እንዴት ሰነበታችሁሳ!

                 እኔ የምለው…ይሄ የቡሄ ነገር… ክፈት በለው በሩን የጌታዬን ክፈት በለው በሩን የእመቤቴን ይባል የነበረው…‘ጌታዬ’ና ‘እመቤቴ’ የተባሉት ቃላት ምነዋ ‘ተሰረዙሳ! አሀ…ከዘንድሮ የእጅ አዙር “ጌታዬ”፣ “እመቤቴ” የበፊቱ እኮ ‘ግልጥና ግልጥ’ ነበራ! ስሙኝማ…የቃላት ነገር ካነሳን አይቀር…እንግዲህ የአዲስ ዓመት ዋዜማም አይደል! እናማ…ከወዲሁ የሆነ…አለ አይደል…በሆነ ጉዳይ ‘ፋና ወጊ’ ምናምን ነገር መሆን አምሮኛል፡፡ ታዲያላችሁ…የዘንድሮ የስብሰባ ቋንቋችን ለምን በአዳራሽና በቲቪ መስኮት ተወስኖ ቀረ የሚል ቁጭት ከዕለታት አንድ ቀን ሊያድርብኝ እንደሚችል ይታወቀኛል፡፡ እናማ…እዛ ሳንደርስ የዓመቱን አስተዋጽኦዬን ባደርግ ምን ይለኛል!…ልክ ነዋ…. እነኛን ቃላት ተጠቅሜ “አይ ላቭ ዩ ሞር ዛን አይ ካን ሴይ” ምናምን ብልስ! “እንትናዬ…ከእኔ ለመለየት መወሰንሽን የነገርሽኝ ዕለት የክርክርሽ አካሄድ ኋላ ቀርና የአፍራሽነት ባህሪይ የተጠናወተው ነበር፡፡

ያነሳሻቸውን ነጥቦች አንጻራዊ በሆነ መልኩ በከፊል ብቀበላቸውም የተንሸዋረረ እይታ እንዳለሽ ግን ሳልጠቅልሽ አላልፍም፡፡ እናማ…እኔን የማንገዋለል ሀሳብ የመጣልሽ ለነገሩ ልዩ ትኩረት ሰጥተሽ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር መክረሽበት ሳይሆን ከግንዛቤ እጥረትና ከልምድ ማነስ መሆን አለበት፡፡ ዙሪያሽን ያሉ የተሳሳተ መረጃ እየሰጡ ሰላምና መረጋጋትሽን የሚረብሹትን ሰዎች ማንነት በንቃት በመከታተል አፍራሽ ምክራቸውን መዋጋት ይኖርብሻል፡፡ እንደ እውነቱ ወሬ ከሚለቅም….ብር የሚለቅም ይሻልሻል ብለው የመከሩሽ ምክር ውሀ የሚያነሳ አይደለም፡፡ ያንቺን አመጡና ለእኔ ነገሩና የእኔን ወሰዱና ለአንቺ ነገሩና ተደላድለው ተኙ አለያዩንና ሲባል ሰምተሽ የለ…” ይሄ ደብዳቤ ገና ከጅምሩ ጠብ፣ ጠብ አለውሳ! “በእርግጥ…በእኔ በኩል አንዳንድ ችግሮች እንዳሉብኝ ግንዛቤ ወስጃለሁ፡፡ ትንሽ ትንሽ መጠጥ ቢጤ መቀማመሴ በቤታችን የመልካም አስተዳደር ሂደት እንቅፋቶች እንደፈጠሩ ይገባኛል፡፡

ግን ደግሞ እንደምታውቂው ዘንድሮ የሚመስሉኝን ሰዎች ሰብስቤ የጋራ ግንባር መፍጠር ካልቻልኩ የበይ ተመልካች ሆኜ መቅረቴ ነው፡፡ ትዝ ካለሽ አንቺን በእኛ ቱባ ሰውዬ የጠረጠርኩሽ ጊዜ ሁኔታውን ያጣሩልኝ የትምህርት ቤት ጓደኞቼና የሰፈር አብሮ አደጎቼ ሳይሆኑ የ‘ፉት’ ቤት ወዳጆቼ ነበሩ፡፡ የዘንድሮ ቅልቅል ደግሞ በዘመድ ጉባኤ ሳይሆን እንደምታውቂው በ‘ፉት’ ዙሪያ ነው፡፡ በአቅሜ አገር በቀሏን ብራንዲ ምናምን በመጠጣቴ የዘላቂ ግብ ችግር እንዳለብኝ መስሎ ሊታይሽ ይችላል፡፡ ሆኖም በእኔ በኩል እነኚህን መጠጦች የምጠጣው ለአገር በቀል ምርቶች ባለኝ ቀናኢነት ነው፡፡ ሆኖም ያመንኩባቸውን ችግሮች ለመቅረፍ ትኩረት ሰጥቼ እየሠራሁ እገኛለሁ፡፡” ልክ ነዋ…ከተማዋን ሲያዩዋት ‘ፉት’ ማለት ‘የሚቀረፍ ችግር’ መሆኑ ቀርቷላ! እኔ የምለው ህዝቤ ከወሩ ውስጥ ሠላሳ ሰባት ቀን የሚጨልጠው ፈረንካው ከየትኛው ጫፍ ነው የሚቆረጠው! የምር… ግራ ግብት ብሎናል፡፡” (አጽንኦት የእኔ! ቂ…ቂ…ቂ…) “የአንቺን ፈጣን እሺታ ለማስገኘት የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ነድፌ ለተግባራዊነታቸው እየተንቀሳቀስኩ ነው፡፡ ለዚህም በሌሎች ሰዎች ተሞክረው ውጤታማ የሆኑ ስትራቴጂዎችን እየፈተሽኩ ነው፡፡

በዚህ በኩል የፈረንሳይ ተሞክሮ ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል በደረሰኝ ጥቆማ መሰረት ድረ ገጾችን እየፈተሽኩ መሆኔን ሳበስርሽ በደስታ ነው፡፡ “ስሚኝማ…አፍ አውጥተሽ አትናገሪ እንጂ እኔ ስጠረጥር ‘ነገርዬው’ ላይ ያለኝ ኋላ ቀርና ያረጀ ያፈጀ አተገባበር ያስከፋሽ ይመስለኛል፡፡ በመሆኑም የፈጠራ ክህሎቴን ተጠቅሜና አግባብነት ያላቸውን ቪዲዮዎች ተመልክቼ በአዲስ አቀራራብ ለመምጣት ተነሳሽነቱ እንዳለኝና ችግሩን በሂደት እንደምቀርፈው ስገልጽልሽ ስጋትሽን እንደሚያስወገደው እርግጠኛ ነኝ፡፡” እንትናዬ… የፌስቡክ ፍሬንዶችሽ ስንት ሺህ ደረሱ! ልክ ነዋ…እኔ እኮ የምለው ዕድሜ ልካቸውን በኖሩበት ሰፈር አምስት ወዳጅ የሌላቸው ሰዎች ዕድም ለፌስቡክ አምስት ሺ የፌስቡክ ወዳጆች አሏቸው፡፡ (ሀያ ከማትሞሉት የፌስቡክ ፍሬንዶቼ የተወሰናችሁ ሰሞኑን ስለምትቀነሱ ቅር እንዳይላችሁማ!) “እናልሽ…የእኔና የአንቺን ጉዳይ ከግብ ለማድረስ ራሴ በራሴ የተቀናጀ ርብርብ አደርጋለሁ፡፡

ታዲያልሸ… እኔ የሚሌኒየም ግብ የአሥር ዓመት ዕቅድ ምናምን እንደሌለኝ ልብ በይ፡፡ ይህ ደብዳቤ በደረሰሽ በማግስቱ ምሳ ሰዓት ላይ እትዬ ሁሉአገርሽ ፍርፍር ቤት እንገናኝ። እንደ ድሮ ‘እኔ እንጀራ ሳይሆን ጸጉሬን ነው ማፈርፈር የምፈልገው’ የምትዪውን ኋላ ቀር አስተሳሰብ ወደዛ አሸቀንጥሪ፡፡” ዐቢይ ነጥብ ማለት ይሄ ነው፡፡ ድጋሚ የሚጠይቅ ድጋሚ ሲጠየቅ እሺ ማለት አለበታ! “ሌላ ደግሞ በወር ሁለት ጊዜ የነበረው የክትፎ ፕሮግራም እንደሚሰረዝ እወቂ፡፡ ሁሉም ነገር በቁጠባ ሆኗል፡፡ አገሪቷ በሌላት ገንዘብ ያለችውን አብቃቅቶ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ቀበቶ ማጥበቅ ሲባል ሰምተሽ የለ! እኔም ቀበቶዬን አጥበቂያለሁ፡፡ ቀበቶዬን ማጥበቄ ምንም እንኳን ገንዘብ ባያመጣልኝ ሆዴ ውስጥ ክፍት የሆነውን ስፍራ ይቀንሰዋል፡፡ ይህም ማለት የወር ወጪዬ ላይ ሚዛን የሚደፋ ለውጥ ያስመዘግባል ማለት አይደል!” ሚዛን የሚደፋ ለውጥ ናፈቀንማ! “እንደገና የጋራ ግንባር በምንፈጥርበት ጊዜ ወጭሽንም ቀንሺልኝ፡፡

ይሄ ጸጉር መደገሚያ ምናምን የምትይው ኋላ ቀርና እኔ ብቻ ማለት እንደሆነ ተረጂው። ሴቱ አንዴም መሠሪያ አጥቶ ጸጉር ሁሉ የብረት ድስት መፈግፈጊያ ሽቦ ሆኗል እሜቲት ድጋሚ ያስፈልግሻል። ለጸጉር መደገሚያ እንደምትዪው ሁሉ ምነዋ አንቺን ለሌላው ነገር ድጋሚ ስትጠይቂ ‘ድሮም መጥፎ ዕድሌ ነው’ እያልሽ የምታማርሪው!” የምናማርርባቸውን ነገሮች ይቀንስልንማ!” “እንግዲህ በመካከላችን ያለውን ልዩነት ለማጥበብ ግማሽ መንገድ ድረስ ሄጃለሁ፡፡ እሺ ካልሽ መልካም፣ አሻፈረኝ ካልሽ ደግሞ መንገዱን ከፈለግሽ ጨርቅ ከፈለግሽ አቡጀዴ ያድርግልሽ፡፡” “እናማ…የእኔዋ እንትናዬ አንድ የማረጋግጥልሽ ነገር ቢኖር በምንም አይነት ወደዛ ለአምስት ሰዓት ቀጠሮ በዘጠኝ ሰዓት ትመጪበት ወደነበረው ጨለማ ዘመን ከእንግዲህ አንመለስም፡፡ በአሁኑ ጊዜ በከተማዋ ልዩ ልዩ ክፍሎች እየተካሄደ ያለው የእንትናዬዎች ነጠቃ አላሳሰብኝም አልልም፡፡ አንቺ እንኳን የሚነጥቅሽ መጥቶ “ሊነጥቁኝ ለሚፈልጉ የወጣ የትብብር መልእክት!” የሚል ማስታወቂያ በኤፍ.ኤም. ብትለቂም አይገርምም፡፡

ለዚህ ነው ካለፈው ስርአት ኋላ ቀር አስተሳሰብሽ አላቅቄ ወደ ‘እንደዘመነችው’ አዲስ አበባ ላዘምንሽ እየጣርኩ ያለሁት፡፡” በወሬ ሳይሆን በአስተሳሰብ የምንዘምንበትን ጊዜ ያቅርብልንማ! “የሆነች የቅኔ መጽሐፍ ሳገላብጥ ያየሁትን ልንገርሽ። ምን ትላለች መሰላችሁ… ‘ቂፍ፣ ቂፍ ያሰኘሽ እንደ ቄብ ዶሮ፣ ለመከራ ለአሳርሽ ኖሮ፡፡’ አሪፍ አባባል አይደል! ‘ጦቢያ’ ውስጥ አሳርና መከራ ቅርብ ስለሆኑ ቂፍ ቂፍ አታብዥማ! ዘንድሮ እንዳንቺ በምኑም በምናምኑም እንደ ቄብ ዶሮ ‘ቂፍ፣ ቂፍ’ የሚያሰኘው ሰው በዝቷል፡፡ ችግሩ ግን ‘ቂፍ፣ ቂፉ’ ለአሳርና ለመከራ እንደሆነ አለማወቁ! “አሁን መጨረሻ ላስገነዝብሽ የምፈልገው አንድና አንድ ነገር ብቻ ነው፣ ይህ አሻፈረኝ የምትዪው ግትርነትሽ ከእንግዲህ እኔ ዘንድ ዋጋ አይኖረውም፡ ወይ አብረሽ ትጓዣላሽ ወይም ባቡሩ ትቶሽ ይሄዳል፡፡

(ይህ አባባል የሸገርን ቀላል ባቡር አይመለከትም፡፡)” ስሙኝማ…ይሄ ደብዳቤ በእስከሪፕቶ ሳይሆን በወይራ ሽመል የተጻፈ አይመስልም! ልክ ነዋ…አንዳንድ መግለጫዎችና ቃለ መጠይቆች በወይራ ሽመል የተጻፉ እየመሰሉን ተቸገርና! ስሙኝማ…የ“አይ ላቭ ዩ ሞር ዛን አይ ካን ሴይ” ደብዳቤ በዘመኑ ቋንቋ ለመተካት የመጣልኝን ሀሳብ ደግሜ እያሰብኩበት ነው፡፡ አሀ…የፍቅር ደብዳቤ ሳይሆን የጦርነት አዋጅ ምናምን መሰለብኛ! “የውቅያኖስ ጥልቀቱ፣ የፀሐይ ሙቀቱ፣ የጨረቃ ድምቀቱ…” የምትለው ለካስ አሪፍ ነበረችሳ! እንደ ቄብ ዶሮ… “ቂፍ፣ ቂፍ…” ከሚያሰኙ ነገሮች ይጠብቅንማ! ደህና ሰንብቱልኝማ!

Published in ባህል

            መርካቶ የሚገኘው አዲስ ከተማ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ተማሪዎቹ በሥነ ግጥም የሚሳተፉበት ውድድር አዘጋጅቶ ነበር፡፡ ተማሪዎቹ ግጥም እንዲጽፉበት የተሰጣቸው ርዕስ “መምህር” የሚል ነበር። አሸናፊዎቹ በተሸለሙበት መድረክ 20 ያህል ተማሪዎች ግጥሞቻቸውን ለታዳሚው አቅርበዋል፡፡ የዳኞችን ብቻ ሳይሆን የታዳሚዎችንም ቀልብ ስቦ በአንደኛነት የተሸለመው ተማሪ ግጥም፤ የአስተማሪን ታላቅ ሰውነት የገለፀው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በማነፃፀር ነበር፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በተንቀሳቀሰባቸው 33 ዓመታት ፍቅርን፣ ሰላምን፣ መቻቻልን፣ ቅንነትን፣ በጎነትን፣ ትህትናን፣ መልካምነትን … አስተምሮ ያለፈ ታላቅ ሰው ቢሆንም በዓለም ታላላቅ የሹመት ስሞች በአንዱም አልተጠራም የሚል መልእክት አንፀባርቋል ግጥሙ፡፡ ክርስቶስ በዘመኑ ብዙዎችን ከደዌያቸው ቢፈውስም ሐኪም አልተባለም፡፡ በባህር ላይ ብዙ ተአምራትን ቢፈፅምም ካፒቴን ተብሎ አልተሰየመም፡፡

ለብዙ ውስብስብና ፈታኝ ጥያቄዎች አጥጋቢና አስገራሚ ምላሾችን ቢሰጥም ፈላስፋ የሚል ማዕረግ አላገኘም፡፡ በኃይልና በጉልበት የመጡበትን ሰዎች በብልሐት ድል ቢነሳም ጄነራል የሚል ማዕረግ አላገኘም፡፡ ውሃን ወደ ወይን ጠጅ ቢለውጥም የሳይንቲስትነት ክብር አልጠየቀም፡፡ የአገር መሪነት አላጓጓውም፡፡ ንጉስነት አልናፈቀውም… በግጥሙ እንዲህ ዓይነት ሃሳቦች ያካተተው ተሸላሚው፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በተከታዮቹና ደቀ መዛሙርቱ ዘንድ ይጠራ የነበረው “መምህር” በሚለው ቃል እንደነበር አመልክቶ የአስተማሪነት ሙያ፤ ለሰው ክብርና ዋጋ የሚሰጡ ሰዎች የሚሰማሩበት፤ ሰውን እንደ ብረት ቀጥቅጠው፣ እንደ እንጨት ልገው፣ እንደ ድንጋይ ጠርበው .. የሚቀርፁና ይህንንም ክቡር ተግባር ለመፈፀም ወደውና ፈቅደው የሚገቡ ልዩ ሰዎች እንደሆኑ በግጥሙ ጠቁሟል፡፡ እንዲህ ዓይነት የግጥም ውድድሮች የመምህርነት ሙያን ለማክበርና ዕውቅና ለመስጠት የሚዘጋጁ ነበሩ፡፡ ጅምሩ አልቀጠለም እንጂ፡፡

አሁን አሁን ደግሞ ለመምህራንና ሙያቸው ትኩረት መስጠት የተጀመረ ይመስላል፡፡ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ኒው ጄኔሬሽን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ፣ 284 ተማሪዎቹን በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ባስመረቀበት ወቅት አስተማሪና የማስተማር ሙያ ልዩ ክብር እንዲሰጠው ያለመ ፕሮግራም አዘጋጅቶ ነበር፡፡ ባለፉት 20 ዓመታት በአገራችን የትምህርትን ተደራሽነት ለማስፋት ብዙ ሥራ ቢሰራም ጥራቱን በተመለከተ ብዙ ጥያቄዎች እነደሚነሱ ይታወቃል። በመምህርነት የላቀ ውጤት ያስመዘገቡትን መሸለም የትምህርት ጥራቱን ለማሻሻል የራሱን አስተዋፅኦ ያበረክታል በሚል ዓላማ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ መምህራንን እያወዳደረ መሸለም ከጀመረ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ የትምህርት ጥራት ውድቀትን በተመለከተ የዩኒቨርሲቲ መምህራን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መምህራንን፣ እነሱ ደግሞ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መምህራንን፣ እነዚህም ወደ ታች እያዩ በመዋዕለ ህፃናት ትምህርት ቤቶች ያለውን አሰራር እንደሚከስሱ በተጠቆመበት ያለፈው ሳምንት የሽልማት ፕሮግራም፤ መካሰስና መወነጃጀል ለችግሩ መፍትሔ እንደማይሆን፣ ለመማር ማስተማሩ ሂደት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተባብረውና ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው ተገልጿል፡፡

ኒው ጄኔሬሽን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅም በራሱ ተቋማት ያሉ መምህራንን ብቻ ሳይሆን ከአገሪቱ ዘጠኝ ክልሎች ተመርጠው የመጡለትን መሸለም የጀመረው ለለውጡ የድርሻውን ለመወጣት እንደሆነ ተነግሯል፡፡ የአስተማሪነት ሙያ ታላቅ መሆኑን ለማሳየት፣ መምህራንን ለማመስገንና ለመምህራን ውለታ ዕውቅና ለመስጠት በዚሁ ዓመት ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ያከናወነው አንድ ተግባር አለ፡፡ ዩኒቨርሲቲው የተመሰረተበትን 60ኛ ዓመት ባከበረበት ባለፈው ሰኔ ወር “የስልሳ ገጾች ወግ” በሚል ርዕስ ታትሞ የተሰራጨው መጽሐፍ፤ የዩኒቨርሲቲውን መምህራን ሰፊ ሽፋን ሰጥቶ ያስተዋውቃል፡፡ በጋዜጠኛ አብርሃም ዘሪሁን የተዘጋጀው 338 ገፆች ያሉት ዳጎስ ያለ መፅሃፍ፤ የመጀመሪያ ክፍል ከጎንደር ከተማ ታሪክ ባሻገር፣ ጎንደር ዩኒቨርስቲ ከየት ተነስቶ ለዛሬ እንደደረሰ፤ በዩኒቨርሲቲ ያለው የመማር ማስተማር ሂደት ምን እንደሚመስል፤ የዩኒቨርሲቲው የተለያዩ የትምህርት ክፍሎች እንቅስቃሴ፤ ስለ ዩኒቨርሲቲው የምርምር ስራዎችና ለህብረተሰቡ ስለሚሰጠው አገልግሎቶች በስፋት ይገልፃል፡፡ “መውለድና መኖር” በሚል ንዑስ ርዕስ የቀረበው የመፅሐፉን ግማሽ የያዘው ሁለተኛ ክፍል ደግሞ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ያስተማሩና በማስተማር ላይ የሚገኙ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ያላቸው አስር መምህራንን ታሪክ ያስነብባል፡፡

የመጽሐፉ አዘጋጅ ጋዜጠኛ አብርሃም ዘሪሁን፤ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ መምህራኑን ማስተዋወቅ ከመጀመሩ በፊት ስለመምህራንና ሙያው ታላቅነት እንዲህ ይላል፡- “መውለድ በራሱ የህይወት ግብ አይደለም። መውለድ ከሚባለው ተፈጥሯዊ ምስጢር በኋላ ብዙ እውነታዎች አሉ፡፡ መውለድ በራሱ ለሰው ልጅ ብቻ የተሰጠ ገፀ በረከት አይደለም፡፡ ያም ሆኖ የሰው ልጆች ውልደት ከማንምና ከምንም በላይ ራሱን የቻለ ትርጉም አለው፡፡ ያለ ምክንያትና ትርጉም የተፈጠረ ማንም የለም፡፡ በተለይ የሰው ልጅ የሚወለደው (የሚፈጠረው) በምክንያትና በትርጉም ነው፡፡ እርግጥ ነው የሁላችንንም ውልደት ምክንያት አንድ አይነት አድርጎ መመልከቱ ሚዛናዊ አይሆንም፡፡ የጋራ የሆኑ የውልደታችን ትርጉሞች ግን የትየለሌ ናቸው፡፡ “እኔ ላወራችሁ የምሻው ግን ተወልደው በመኖራቸው … ኖረውም ትርጉም ያለው ነገር በመስራታቸው፤ ትርጉሙም ከራሳቸው አልፎ ለአብዛኛው ህብረተሰብ ስላንፀባረቀው እንቁዎች ነው፡፡ እነዚህ እንቁዎች ከራስ በላይ ለሆነ ትርጉም መፈጠራቸውን፤ ሲያስቡት በሚቀለው፣ ሲሞክሩት ግን በሚከብደው ዓለም ላይ በተግባር አሳይተዋል፡፡ “በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የስልሳ (60) ዓመት ጉዞ ውስጥ ታሪክ የሰሩ ጀግኖች ሃውልት ላቆም ተነስቻለሁ፡፡ ይህንን ሃውልት ለማቆም ሳስብ ግን ታሪካቸውን የማወራላቸው እንቁዎች ሁሉም በህይወት እያሉ በመሆኑ ኩራት ይሰማኛል፡፡ በእርግጥም በህይወት ያሉ እንቁዎቻችንን የማድነቅ ባህላችንን ማሳደጉ ሳይጠቅመን አይቀርም” በማለት ባለታሪኮቹን ያስተዋውቃል፡፡

የትምህርት፣ የሥራና የቤተሰብ ታሪካቸው የቀረበው አሥሩ ፕሮፌሰሮች፡- የቆዬ አበበ፣ ያሬድ ወንድምኩን፣ ተፈራ አቡላ፣ ይግዛው ከበደ፣ መልኬ እድሪስ፣ ሞገስ ጥሩነህ፣ መንገሻ፣ አድማሱ፣ ጌጡ ደጉ፣ አፈወርቅ ካሱ፣ ራምስ ዋሚ ሲሆኑ ፕሮፌሰር ራምስ ህንዳዊ ናቸው፡፡ አስተማሪነትና የማስተማር ሙያን የሚያወድሱ ንግግሮች፣ ግጥሞች፣ የአድናቂ ምስክርነቶች … በተለያዩ ጊዜያት ቀርበዋል፡፡ ኒው ጄኔሬሽን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅን ጨምሮ ሌሎች የትምህርት ተቋማት ሙያውንና ባለሙያውን ለማክበር የጀመሩት ጥረት የሚደነቅ ነው። ተጠናክሮም ሊቀጥል እንደሚገባው ይታመናል። መምህራን ትውልዱን የሚያንፁ የሀገር መሰረት መሆናቸውን ተገንዝቦ መሸለምና ዕውቅና መስጠት ልባምነት ነው፡፡

Published in ህብረተሰብ

          ባለፈው ሳምንት የአዲስ አድማስ እትም ዳዊት ንጉሱ ረታ፤ የአማተር የኪነ-ጥበብ ክበባቶቻችንን ጉዳይ አንስቶ እንነጋገርበት ዘንድ ጥሪውን አቅርቧል። ዳዊት በአባቱ ሥም አቋቁሞት በነበረው (በኋላ “እሸት” ወደተሰኘ ማህበር ተቀይሯል) እኔም ተሣታፊ ነበርኩ፡፡ ምንም እንኳን በጀመርኩበት ባልዘልቅም ጥሩ የጥበብ ወዳጅ እንድሆን አስችሎኛል፤ ዳዊት እጄን ይዞ ከኪነ ጥበብ ጋር አወዳጅቶኛል፡፡ እናም ታዲያ እንደነዚያ አይነቶቹ አማተር ክበባት እንደዋዛ የመጥፋታቸው ነገር ቢያሳስበው ዳዊት ብዙ ጠይቋል፡፡ በእኔ እምነት እነዚያ ክበባት የመጥፋታቸው ሰበበ ምክንያት በርካታና ዘርፈ ብዙ ነው፤ በጉዳዩ ላይ መወያየታችን የዘገየ ቢሆንም ምን ቢመሽ ጨርሶ አልጨለመምና፣ ዳዊት በቀደደው ገብቼ ጥቂት የማምንበትን ለማለት እሞክራለሁ፡፡

በከተማችን አዲስ አበባና በሌሎች ክልሎች ወጣቶች ለጥበብ ያላቸውን ፍላጎት፣ ተሰጥዖና ዝንባሌን መነሻ እያደረጉ፣በራሳቸው ተነሳሽነት በት/ቤቶችና ቀበሌ አዳራሾች የተፍጨረጨሩበትና ክበባቶቹ በርክተው የተስተዋሉበት ወቅት እንደነበረ ባይዘነጋም፣ ከ1990ዎቹ አጋማሽ ወዲህ እየተቀዛቀዙ… አሁን አሁን ከእነ አካቴው ጠፍተዋል። በእነዚያ ዓመታት ተሰጥኦና ዝንባሌን መሰረት አድርገው ከጥበብ ጋር በጥልቀት እያስተዋወቁ፣ በሙያዊ ሥነ ምግባር እያነፁ፣ እምቅ ችሎታንና ብቁ ክህሎት እያስታጠቁ፣ ልከኛ ጥበበኞችን ለመድረኮቻችን ያበረክቱ የነበሩ ክበባት ዛሬ ላይ የሉም፡፡ አፍላ ጥበበኞችን የሚኮተኩቱ፣ ጥሩ ባለሙያ የማያመርቱ ክበባት እንዲሁ ዝም ብለው አልከሰሙም፤ ደጋፊ፣ አጋዥና “አለሁ” ባይ እያጡ፣ ተሰባስቦ ጥበብን መከወኛ ሥፍራ እየተነፈጉ፣ ትላንት ኮትኩተው ያሳደጉት የዛሬው ዝነኛም አዙሮ የመመልከት አቅም አጥ ሆኖ፣ ውለታቸውን እየዘነጋ የሚተኩትን ተከታይ ባለተራዎችን ማገዝ የተሳነው የመሆኑን ነገር እንደ አንድ የመክሰማቸው ምክንያት ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡

በእግር ኳስ የስፖርት ሜዳ ተጋጣሚ ቡድኖች ወደ ሜዳ ሲገቡ ታዳጊ ህፃናትን አስከትለው የሚገቡት ለምን ይመስለናል? ተኪነትን ለማጎልበትም አይደል? በአገራችን የጥበብ ሜዳችን ላይስ? ገጣሚና ጋዜጠኛ ነቢይ መኮንን በአንድ ግጥሙ “የሀገሬ ሰው እኮ መሠላል አወጣጥ ያውቃል” እንዳለው፤ የሃገሬ ዝነኛ ከያኒያን መሰላሉን እየወጡ የረገጡትን እየነቀሉ ይሆን? ለአማተር ክበባቶቻችን መክሰምና ለአዳዲስ ክበባቶች አለመፈጠር እንደ ጉልህ ምክንያት ሊወሰድ የሚገባው ሌላ ነገር መንግስታዊ ቸልተኝነትና ዝንጋታ ነው! ጥቂት ማሳያዎችን እንመልከት፡- መንግስት የወጣቶችን የሥራ አጥነት ለመቅረፍ “የጥቃቅንና አነስተኛ ሥራዎች ልማት ፕሮግራም” አዘጋጅቶ እየተገበረ እንደሆነ ይታወቃል። ግን ደግሞ በኪነ ጥበባዊ ሥራዎች ላይ ተደራጅቶ ስለመስራት መንግስታዊ ፕሮግራሙ የሚለው ነገር የለም፤ ቴአትር ለማዘጋጀት፣ የግጥም መፅሐፍ ለማሳተም ወይ ደግሞ ፊልም ሰርቶ ለማሳየት ብድር አይሰጥም… ማበረታቻም የለም፡፡ በመላው አገሪቱ ባሉ ክልሎችና ከተማዎች (እስከታችኛው መንግስታዊ መዋቅር ድረስ) ባህልንና ኪነ-ጥበብን የማስፋፋት ኃላፊነት የተጣለበት በአዋጅ የተቋቋመ “ባህልና ቱሪዝም መ/ቤት” ቢኖርም አማተር ክበባትን ለመፍጠር ሲጨነቅ አይስተዋልም፡፡

በአንድ ወቅት እኔው እራሴ ወደ አዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሄጄ፣ አማተር ክበብ ለመመስረት ሞዴል /መነሻ/ መተዳደሪያ ደንብና ሌሎች መስፈርቶች ጠይቄ ማግኘት አልቻልኩም፤ ግን ደግሞ ካፒታል ኖሮት፣ ንግድ ፈቃድ አውጥቶና ሰፊ በጀት መድቦ ፕሮሞሽንና የፊልም ፕሮዳክሽን በማቋቋም በጥበባዊ ንግድ ስራ ላይ መሰማራት ለሚፈልግ ሰው፣ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ለመስጠት ግልፅ መሥፈርት ወጥቶ፣ ባለሙያ ተቀጥሮ፣ የስራ ሂደት ቢሮ ተከፍቶላት አይቻለሁ፡፡ ይህ ቢሮ በከተማ ደረጃ ከቅርብ አመታት ወዲህ አማተሮች የሚወዳደሩበት የባህል ፌስቲቫል በአመት አንድ ጊዜ ብቻ እያዘጋጀ ይገኛል፤ ለአማተር የኪነ ጥበብ ባለሙያ አፍላ ወጣቶቻችን ነፃና የአጭር ጊዜ የተሰጥኦ ማጎልበቻ የሥልጠና እቅድ ይዞ መስራት እንኳን አልተቻለውም፡፡

ቴአትር ቤቶቻችንም ለአማተሮቹ በራቸው ዝግ ነው፤ የተተመነውን የአዳራሽ ኪራይ ክፍያ መክፈል ካልቻሉ በስተቀር በነፃ ወይም በዝቅተኛ የኪራይ ዋጋ መድረኮቻቸውን አይቸሩም፡፡ በየት/ቤቶቻችን “የተጓዳኝ ትምህርት ክፍል” በሚል የሚኒ ሚዲያ፣ የቴአትርና የሙዚቃ ክበባት ተመስርተው ተማሪዎች ከመደበኛው የትምህርት ክፍለ ግዜ ውጪ ይሳተፉባቸው የነበሩ ቡድኖች ዛሬ የሉም፤ ቢኖሩም በጣት የሚቆጠሩና የተፋዘዙ ናቸው፡፡ በርካታ የሬድዮ ጣቢያዎች፣ ሁለትና ሶስት የቴሌቪዥን ቻናሎች እያሉን ለአማተሮች የሚሆን ነፃ የአየር ሠዓት ግን የለንም፤ የተለያዩ የኪነ-ጥበብ (በተለይ የሥነ-ፅሁፍ) ሥራዎች በአማተሮች አማካኝነት ይቀርቡባቸው የነበሩ ማዕከላት እነ ፑሽኪን (የሩሲያ የሳይንስና ባህል ማእከል)፣ ኢትዮ አሊያንስ ፍራንሴስ እና ገተ… እንኳን ዛሬ ዛሬ ተፋዘዋል፡፡ እነዚህም ቢሆኑ በውጭ ሀገራት ኤምባሲዎች መልካም ፈቃድ የተቋቋሙ ማዕከላት መሆናቸውን ስናስተውል እንደ ሀገር አማተሮች ምን ያህል እንደተዘነጉ እንረዳለን፡፡ አስገራሚው ነገር ደግሞ ትላንት ከትላንት ወዲያ የመከወኛና የመሰባሰቢያ ሥፍራ ባልነበረበት እንደ አሸን የፈሉ ክበባት፣ ዛሬ በተለይ በከተሞቻችን “የወጣት ማዕከላት” በየመንደሩ ተገንብተው እያለ፣ የማዕከላቱ አዳራሾች ተሰብሳቢ ጭብጨባ እንጂ የአማተሮቻችን ድምፅ አይሰማባቸውም፡፡

ለምን?? የሙያ ማህበሮቻችንስ? የደራሲያን ሆነ የፊልም ሰሪዎች፣ የሙዚቀኞች ይሁን የቴአትር ባለሙያዎች… ብቻ የቱም ይሁን፤ ጊዜ ቀንቷቸው በፕሮፌሽናል መድረኩ ላይ ላሉት እንጂ ለአማተሮቹ ምን ቦታ አላቸው? ምንም! በደራሲያን ማህበር አባል ለመሆን መፅሐፍ ማሳተም እንጂ መፃፍና ሥነ-ፅሁፋዊ ተሰጥኦ እንደመስፈርት አይቆጠርም፡፡ የትላንቶቹ አማተር ክበባት ለበርካታ ማህበራዊ ችግሮቻችን መወገድ ጉልህ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡ የኤችአይቪ/ኤድስ በሽታ ዛሬ ላይ ስርጭቱ እንዲቀንስ፣ ታማሚዎች ላይ ይደርስ የነበረው አድሎና መገለል እንዲቀር እነዚያ ክበባት መዝሙር ዘምረው፣ ድራማ ሰርተውና ግጥም ፅፈው ህብረተሰቡ አዎንታዊ የባህርይና የአመለካከት ለውጥ እንዲያመጣ ተረባርበዋል፡፡ ኤችአይቪ/ኤድስ የስርጭቱ መጠን እየቀነሰ ቢመጣም ሌሎች ችግሮች የሉብንም? የባህልና ትውፊት መጥፋቱስ? ከምዕራብ ሀገራት በአስገራሚ ፍጥነት እየወረሩን ያሉ መጤና ጎጂ ልምዶችስ?... የአማተር ክበባቶቻችን ጥበባዊ ውጊያ አያሻቸውም? በሁለንተናዊ የ“ህዳሴ” ጉዞ ላይ እንደምንገኝ በተደጋጋሚ ይገለፃል፡፡

ለመሆኑ የ“ህዳሴ ጉዞ” ጥበባዊ እገዛ አያስፈልገውም? በዜጎች ደረጃ የአመለካከት ለውጥ ሳይመጣ ያደገና የበለፀገ ሃገር የትኛው ይሆን? አብዝቶ የሚወራለት “ልማታዊ ኪነ-ጥበብ” እንዴትና በማን አማካኝነት ነው ሊሰራ የሚችለው? በአማተሮችና በክበባቶቻቸው አይደለምን? ሀገር ያለወጣት ምንም ናት! መተካካት ደግሞ ተፈጥሮአዊ ህግ ነው! ኖሮ ኖሮ ማለፍ ግድ ነው!... አይቀርም! ስለ ነገው የኪነ-ጥበብ ኢንዱስትሪያችን ሥናስብ፤ ተተኪን ኮትኩቶ ስለማሳደጉ ካልተጨነቅን ነገን ማሰብ ትርፉ ድካም ይሆናል፡፡ የንጉሱ ረታ ልጅ ዳዊት እንዳለው፤ ማንም በነሸጠው ግዜ አሊያ ደግ ገንዘብ ስላለውና መንገዱ አልጋ ባልጋ ስለሆነለት ወይም መልክና ቁመናው ስላማረለት ብቻ ወደ ጥበብ ባህር ዘሎ እየገባ “ልዋኝ” ካለ መንቦጫረቅ ይሆንና ባህሩ ይረበሻል፤ ሲብሥም ሊደርቅ ይችላል፡፡ የባህል ፖሊሲያችን ሊከለስ፣ የጥቃቅንና አነስተኛ ፕሮግራሙም ሊሻሻል፣ የባህልና ቱሪዝም መ/ቤቶቻችንም ቆም ብለው ሊያጤኑ፣ ባለ ጊዜዎቼ “ጥበበኞችም” አንገታቸውን አዙረው ሊመለከቱ ግድ ነው! የጠፉት ክበባት ይመጡ ዘንድ እንትጋ! አዳዲሶቹ አማተሮችም ይወለዱ ዘንድ እናምጥ!!

Published in ህብረተሰብ

የዘንድሮው የጋዜጠኞች ስደት ለማስተባበል አይመችም!

በቅርቡ ፍትህ ሚኒስቴር በአምስት መፅሄቶችና በአንድ ጋዜጣ ባለቤቶችና አሳታሚዎች ላይ የመሰረተው ክስ ብዙ አላስደነገጠኝም፡፡ እኔን ብቻ ሳይሆን ብዙዎችን ያስደነገጠ አይመስለኝም፡፡ በተለይ በቅርቡ ኢቴቪ የሰራውን በግል ፕሬሱ ውልደትና ዕድገት ላይ የሚያጠነጥን ዶክመንተሪ የተመለከተ ፈፅሞ አይደነግጥም፡፡ (የክስ ቻርጅ ማለት እኮ ነው!) የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትና ኢዜአ በግል መፅሄቶች ላይ አሰሩት የተባለው ጥናትም ተመሳሳይ ነው፡፡ (እነ ኢዜአ ላይ ጥናት ላካሂድ ነው!) በነገራችሁ ላይ በጥናቱ ከቀረበው ትንተና በጣም የማረከኝ “የኢኮኖሚውን ዕድገት የካዱ” የምትለዋ ነበረች፡፡ (ሁሉም ክደውታል እኮ!)
እናላችሁ… በመፅሄቶቹ መከሰስ ብዙ ሳልደነግጥ አገር ጥለው ተሰደዱ ሲባል ክው አልኩላችሁ፡፡ የ4ቱ ሲገርመኝ 7ቱ ተደገሙ፡፡ (እንዴት አያስደነግጥ!) እኔማ ቢቸግረኝ … “ስደት” ተፈርዶባቸው ይሆን እንዴ አልኩ - ለራሴ፡፡ በንጉሱ ዘመን “ግዞት” እንደሚባለው ዓይነት! (11 ጋዜጠኞች በሁለት ሳምንት መሰደድ እኮ… በኤርትራም ያልተያዘ አዲስ ሪከርድ ነው!)
እኔ ግን እኒህ ሁሉ ነገሮች ባይፈጠሩ ደስ ይለኝ ነበር፡፡ (አንተ ማነህ? እንዳትሉኝ!) ክሱም፤ ስደቱም፤ እስሩም፣ ውዝግቡም… ወዘተ ማለቴ ነው፡፡ ሌላው ሁሉ ቢቀር ኢቴቪ ደጋግሞ ለሚወተውተን “የአገር ገፅታ ግንባታ” አሉታዊ እንጂ አዎንታዊ አስተዋፅኦ ወይም ተፅዕኖ የለውም እኮ (ልብ አድርጉ! ምኞቴን ነው የተነፈስኩት!)
ባለፈው ዓመት ከኤርትራ ቀጥሎ ጋዜጠኛ በማሰር ከዓለም 2ኛ ደረጃ ላይ ያስቀመጠን ዓለም ዓቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች (CPJ) ዘንድሮ ስንተኛ እንደሚለን አሰብኩና አንጀቴ አረረ፡፡ እኔ ኢህአዴግን ብሆን ምን እንደማደርግ ታውቃላችሁ? CPJ ሪፖርት እስኪያወጣ አልጠብቅም፡፡ ፈጥኜ የራሴን ሪፖርት አወጣለሁ፡፡ “11 ጋዜጠኞች ተሰደውብኛል” እላለሁ። (የዘንድሮው ለማስተባበልም አይመችማ!) እርግጠኛ ነኝ የCPJ ሪፖርት በዚህ ብቻ አያበቃም፡፡ የታሰሩትን 6 ጦማርያንና 3 ጋዜጠኞችንም ማካተቱ አይቀርም፡፡ (“በሙያቸው አይደለም” ሲባል አይሰማማ!) ከዚያም ጋዜጠኞች በማሰርና ለስደት በመዳረግ ኢትዮጵያን ከዓለም 1ኛ አድርጓት ቁጭ ይላል፡፡ ለነገሩ ዓምና ጋዜጠኞችን በማሰር ከዓለም ሁለተኛ የተባልነው “እውነት” ከሆነ፣ ዘንድሮ 1ኛነቱን ማንም አይነጥቀንም፡፡ (በCPJ የግምገማ መነፅር ማለቴ ነው!) ዓምና ጋዜጠኞችን በማሰርና በማሰደድ አንደኛ የወጣችውን ኤርትራን መብለጣችን አይቀርም (ኤርትራ ያሏትን ጋዜጠኞች ዓምና በእስርና በስደት ጨርሳለቻ!)
እናም … እኔ ኢህአዴግን ብሆን ይሄ CPJ የተባለ “የጋዜጠኞች ተሟጋች ነኝ ባይ”፤ ሪፖርቱን ከማውጣቱ በፊት ቀድሜ በጋዜጠኞች አያያዝ ያለሁበትን አቋም እገልፅ ነበር፡፡ (ላስተባብል እኮ ነው!) የታሰሩትን የተሰደዱትን፣ የተከሰሱትን… በቁጥር፤ በፆታ፣ መድቤ ይፋ አደርገዋለሁ (ማን ይፈራል ሞት አሉ!) እርግጥ ነው ኑዛዜ ሊመስልብኝ ይችላል፡፡ (ይምሰላ!) ዋናው ነገር የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ነኝ ባዩን ድርጅት ኩም ማድረግ ነው፡፡ አያችሁ … CPJ እንደኛ አገር የጋዜጠኞች ማህበራት ነገሮችን በጥልቀት አይመረምርም፡፡ ለምሳሌ ብሎገሮች ምድባቸው ከጋዜጠኝነት እንዳልሆነ የሰማሁት ከኢትዮጵያ የጋዜጠኛ ማህበር ፕሬዚዳንት እንጂ ከCPJ አይደለም፡፡ (አያችሁ ልዩነት!)
እስካሁን የምመኘውን ተንፍሼአለሁ፡፡ አሁን ደግሞ የምፈልገውን ልተንፍስ፡፡ እኔ የምላችሁ ግን … “መንግስት ሆደ ሰፊ ነው” ሲባል አልነበረም እንዴ? (ሆደ ሰፊነቱ ለእኛ ነው ለጎረቤት አገር?) ግዴለም ሆደ ሰፊነቱም ይቅር… ግን እንደመንግስት ለግሉ ፕሬስ ማደግና ማበብ ምን አበረከተ? (“የኢቴቪ ዶክመንተሪስ?” እንዳትሉኝ!) ከክስ ቻርጅ በፊት የጋዜጠኝነት ስልጠና፣ የአቅም ግንባታ፣ የሙያ ክህሎት፣ ዎርክሾፕ እኮ ቢቀድም ስደትም እስርም ክስም ባልኖረ ነበር፡፡
ሰሞኑን አንድ ወዳጄ በሬዲዮ ሰማሁ ያለውን ባለ 5 ኮከብ ቅንጡ ወህኒ ቤት ታሪክ አጫወተኝ፡፡ ሌላ ስያሜ ጠፍቶለት ነው እንጂ እስር ቤት ለማለት አንኳን ይቸግራል፡፡ ወህኒ ቤቱ ያሉት መዝናኛዎች … ሲኒማ ቤቱ፣ የጂምናስቲክ ማዕከሉ፣ የመዋኛ ገንዳው፣ የቴኒስ ሜዳው … ግርም ድንቅ የሚሉ ናቸው፡፡ (ወዳጄ እንዳጫወተኝ እኮ ነው!) የወዳጄን ጨዋታ አብራን ስትሰማ የነበረችው የ10 ዓመት ልጁ ምን እንዳለች ታውቃላችሁ? “በእናትህ ባቢ.. እዛ አገር ሄደን እንታሰር” አይገርምም ለመታሰር የሚያስመኝ ወህኒ ቤት… ለነገሩ ለባለ 5 ኮከብ ወህኒ ቤት ባለ5 ኮከብ ወንጀለኛ ያስፈልጋል፡፡
ከባለ 5 ኮከብ ወህኒ ቤት በቀጥታ የምንሻገረው ወደ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጎራ ነው፡፡ እኔ የምላችሁ … የኢዴፓ ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ሙሼ ሰሙ ራሳቸውን ከፖለቲካ ፓርቲ ማግለላቸውን እንዴት አያችሁት? (የጥሞና ጊዜ ፈልገው እኮ ነው!) እኔማ የእሳቸውን ዜና ባለፈው ሳምንት እዚሁ ጋዜጣ ላይ ሳነብ፣ ከዚህ ቀደም ራሳቸውን ከፓርቲ ፖለቲካ ያገለሉ ሰዎች በዓይነ ህሊናዬ ይመጡብኝ ጀመር፡፡ የኦፌዴኑ አቶ ቡልቻ … የመድረኩ አቶ ስዬ (የቀድሞው የህወሃት ታጋይና የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር) .. የአንድነቷ ወ/ት ብርቱካን (የሃርቫርድ ምሩቅ!) … የመኢአዱ ኢንጂነር ኃይሉ (ቆፍጣናው አዛውንት!)… የአንድነት ሊቀመንበር የነበሩት ዶ/ር ነጋሶ (የቀድሞ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት!) የኢዴፓው የቀድሞ መሪ አቶ ልደቱ (የሦስተኛ አማራጭ አቀንቃኝ!) ሌሎችም የዘነጋኋቸው ሳይኖሩ አይቀሩም፡፡ እኒህ ሁሉ በፈቃዳቸው የተገለሉ ናቸው፣ ከጦቢያ የፖለቲካ ንፍቀ ክበብ!
እርግጥ ነው አንዳንድ ከፖለቲካው ተገልለው እቤታቸው መቀመጥ ያለባቸው “ፖለቲከኞች” (በመጃጃት፣ ባለመብሰል፣ በስልጣን ሱሰኝነት፣ በእብሪተኝነት… ዝርዝሩ ብዙ ነው!) ችግሩ ግን ምን መሰላችሁ? እራሳቸው ካልፈለጉ በስተቀር ማንም ሊያገላቸው አይችልም፡፡ አንዳንዴ ምን እላለሁ መሰላችሁ? ምነው የኢህአዴግን የመተካካት ስልት ተቃዋሚ ፓርቲዎች በኮረጁት! (አጉል ምኞት መሆኑ ይገባኛል!) በነገራችሁ ላይ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ከሞቱ በኋላ ኢህአዴግም መተካካትን አንስቶት አያውቅም እኮ። (ከእሳቸው እረፍት በኋላ የተተካካ አላየሁማ!) እርግጥ ነው… ብዙ የፓርቲው አባላት በመንግስት የኃላፊነት ቦታቸው ላይ በፈፀሙት ሙስና ወህኒ  ወርደዋል፡፡ (ወህኒ መውረድ ግን መተካካት አይደለም!)  
ሳልዘነጋው አንድ ወግ ላውጋችሁ፡፡ አንድ ባልደረባዬ ሁነኛ ጉዳይ ኖሮባት ወደ አንድ የመንግስት መ/ቤት ትሄዳለች - ሰሞኑን ነው፡፡ ለከሰዓት ይቀጥሯታል፡፡ ከሰዓት ተመልሳ ስትሄድ ግን “ለመለስ ሻማ ለማብራት ልንሄድ ነው” አሉና ጥለዋት ውልቅ አሉ፡፡ (የጠ/ሚኒስትሩን ሁለተኛ ሙት ዓመት ለመዘከር ነው!) መለስ ግን የትኛውን የሚመርጡ ይመስላችኋል? ሻማ እንዲበራላቸው ወይስ ሥራ በአግባቡ እንዲሰራ? (እኔ ከኢህአዴግ አላውቅም!)
ወደ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጎራ ልመልሳችሁ። ራሳቸውን ከፖለቲካ ፓርቲ ያገለሉ ፖለቲከኞችን ሳስብ ምን ይታየኛል መሰላችሁ? ተስፋ መቁረጥ! በአገራቸው… በፓርቲያቸው .. በኢህአዴግ… በስልጣን… በራሳቸው ወዘተ… ተስፋ የቆረጡ እየመሰለኝ እኔም ተስፋ እቆርጣለሁ፡፡ እኔ ግን ተስፋ ብቆርጥም መፃፍ አላቆምም። ሌላው ቢቀር ተስፋ ስለቆረጡ ፖለቲከኞች እፅፋለሁ፡፡ (ፖለቲከኞች እንጂ ፀሃፊዎች ተስፋ አይቆርጡም እኮ!) እኔ የምለው ግን ከኢህአዴጎች ውስጥ ራሳቸውን በራሳቸው ከፖለቲካ የሚያገሉ የሉም እንዴ? (አይፈቀድ ይሆናላ!)
እናላችሁ… በዕድሜ ገፋ ያሉት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በከንቱ ከሚለፉ ራሳቸውን ከፖለቲካው ማግለላቸው ለሁላችንም (ለእነሱም … ለእኛም… ለአገርም … ለዓለምም!) የሚበጅ ይመስለኛል፡፡ ለምን መሰላችሁ? አልሆነላቸውማ! (ሥልጣኑን ማለቴ ነው!) ከምሬ እኮ ነው … የአብዛኞቹ ተቃዋሚዎች ግብ ወይም ግብግብ  ኢህአዴግን ከስልጣን አውርዶ ስልጣን መያዝ ብቻ ነው፡፡ (ሥልጣንና ሥልጣን ብቻ!) ለእነሱ ህዝቡን የሥልጣን ባለቤት ማድረግ እኮ ይሄ ነው! ችግሩ ግን ይሄ በቅርቡ እውን የሚሆን አይመስልም፡፡ (ኢህአዴግም የዋዛ አይደለማ!) ተቃዋሚዎች (ያውም ቱባ ቱባዎቹ!) በ97 ምርጫ ህዝቡ የሰጣቸውን ዕድል ከኢህአዴግ ጋር ተባብረው እንዴት አፈር ድሜ እንዳስበሉት አይተነዋል፡፡ (“የወጋ ቢረሳ…” አሉ!) ግባቸው ሥልጣን ብቻ ነው ያልኩት እንደ ኢህአዴግ ልኮንናቸው ፈልጌ እንዳይመስላችሁ፡፡ (ምን ልጠቀም?) እውነት ስለሆነ ብቻ ነው፡፡ ይሄውላችሁ .. ተቃዋሚዎች (ሁሉም አልወጣኝም!)
በአገሪቱ ውስጥ ዲሞክራሲ እንዲሰፍንና እንዲፋፋ ቢፈልጉ ኖሮ ቤተመንግስት ብቻ ሳይሆን ፓርላማ መግባትም ያጓጓቸው ነበር፡፡ (ጉጉት ፓርላማ አያስገባም እንዳትሉኝ!) ኢህአዴግ በሚለው መንገድ ባይሆንም ዲሞክራሲ ሂደት መሆኑን ተረድተው በአንድ ዙር ምርጫ ሁሉም ነገር ካልተለወጠ ብለው አይፈጠሙም ነበር፡፡ በዚያ ላይ በየፓርቲው ውስጥ የምናየውና የምንሰማው ግጭትና ፍጭት፣ መናቆርና መቃቃር፣ መወጋገዝና ዱላ መማዘዝ… (ሰሞኑን በመኢአድ የተከሰተውን ልብ ይሏል!) ለዲሞክራሲና ለስልጡን የፖለቲካ ባህል ዝግጁ  አለመሆናቸውን ይጠቁመናል፡፡ ሰው እንዴት ዘመኑን አይመስልም? (21ኛውን ክ/ዘመን ማለቴ ነው!) እናላችሁ… በፖለቲካው ውስጥ ያረጁ ትያፈጁት ቦታ ሲለቁ… ገለል ሲሉ… ግሩም ነው (አይሉም እንጂ!) ነገር ግን እንደ እነ አቶ ሙሼ ሰሙ፣ ወይም ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ያሉት ከፖለቲካው ንፍቀ ክበብ መገለላቸው የሳሳውን የተቃዋሚ ጎራ ጭርሱኑ ኦና እንዳያደርገው ያሰጋል (ወላድ በድባብ ትሂድ እንዳትሉኝ!)
እኔ የምለው ግን… ይሄ ትግልን ዳር ሳያደርሱ  ትምህርቴ… ትዳሬ… ቤተሰቤ… የሚሉት ነገር አግባብ ነው እንዴ? (በትምህርት ሰበብ ስንቱ ሸወደን?!) እርግጠኛ ነኝ የአውራ ፓርቲ አባል ቢሆኑ ኖሮ ይሄ ሁሉ ሰበብ የለም ነበር፡፡ (በኢህአዴጎች አይተነዋላ!) የሆነ ሆኖ ግን ማስገደድ አንችልም፡፡ ራሳቸውን ከፖለቲካ ያገለሉትን ሁሉ “መንገዱን ጨርቅ ያድርግላቸው” ብለናል! (ምርቃት ነው ተብሎ የለ!)

Saturday, 23 August 2014 11:00

የፍቅር ጥግ

ስለህፃናት
ህፃናት የላቀ አክብሮት ይገባቸዋል፡፡ በአዕምሮህ ውስጥ ክፉ አሳፋሪ ነገር ካለ፣ የልጅህን ለጋ ዕድሜ

እንዳትዘነጋው፡፡
ጁቬናል
(ሮማኒያዊ ገጣሚ)
ልጅ ትክክል የመሆን ብቻ ሳይሆን የመሳሳትም መብት እንዳለው ያወቀ ጊዜ ወደ አዋቂነት ተሸጋግሯል፡፡
ቶማስ ስዛስዝ
(ትውልደ ሃንጋሪ አሜሪካዊ  የሥነ-አዕምሮ ባለሙያ)
ልጃችሁ ስለጠላው ብቻ ምግብ የግድ አስፈላጊ ነው ማለት አይደለም፡፡
ካታሪን ዋይትሆርን
(እንግሊዛዊ ጋዜጠኛና ፀሐፊ)
የዘመድ ልጆች በዙሪያችን መኖራቸው ጥሩ ነገሩ፣ ወደቤታቸው መሄዳቸው ነው፡፡
ክሊፍ ሪቻርድ
(ትውልደ ህንድ እንግሊዛዊ የፖፕ
ሙዚቃ አቀንቃኝ)
ሁሉንም ልጆቼን  እወዳቸዋለሁ፤ አንዳንዶቹ ግን ደስ አይሉኝም፡፡
ሊሊያን ካርተር
(አሜሪካዊት ነርስና የጂሚ ካርተር እናት)
ህፃናትን በተለይ ሲያለቅሱ እወዳቸዋለሁ፤ ያኔ አንድ ሰው መጥቶ ይወስዳቸዋል፡፡
ናንሲ ሚትፎርድ
(እንግሊዛዊ ፀሐፊ)
ውድ ተመልካቾች፤ ትያትሩ ካልቆመ በስተቀር ህፃኑ ለቅሶውን መቀጠል የሚችል አይመስልም፡፡
ጆን ፊሊፕ ኬምብል
(እንግሊዛዊ ተዋናይ)
(የሚተውንበት ትያትር በአንድ ህፃን ተደጋጋሚ ለቅሶ ሲረበሽ ለተመልካቹ የተናገረው)
ፈፅሞ ልጆች እንዳይኖሩህ፤ የልጅ ልጆች ብቻ!
ጐሬ ቪዳል
(አሜሪካዊ ደራሲና ወግ ፀሐፊ)

Published in ጥበብ

                 የምስራቅ አፍሪካ የእጅ ኳስ ሻምፒዮና በኢትዮጵያ የወጣቶች ስፖርት አካዳሚ በሚገኘው ዘመናዊ ጅምናዚዬም በነገው እለት ሊጀመር ነው። ውድድሩን ዓለምአቀፉ የእጅ ኳስ ፌዴሬሽን (IHF) የሚያዘጋጀው ሲሆን በአፍሪካ ደረጃ በዞን አምስት የሚገኙት ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ ሱማሌና ሱዳን ይሳተፉበታል፡፡ አራቱ አገራት ‹‹ቻሌንጅ ትሮፊ›› በሚል ስያሜ ከነገ ጀምሮ እስከ ሳምንቱ አጋማሽ የሚካሄደው የምስራቅ አፍሪካ የእጅ ኳስ ሻምፒዮናው ላይ የሚካፈሉት በሁለቱም ፆታዎች ዕድሜያቸው ከ19 ዓመት በታች የሆኑ ስፖርተኞችን በማስመዝገብ ነው፡፡ በሁለቱም ፆታዎች ሻምፒዮን የሚሆኑት ብሄራዊ ቡድኖች የምስራቅ አፍሪካ ዞንን በመወከል በአፍሪካ የእጅ ኳስ ሻምፒዮና ላይ ተወዳዳሪ ይሆናሉ፡፡ በትንሿ ስታድዬም ዙሪያ እና በአራት ኪሎ የስፖርት ማዕከል ለሚገኙ የስፖርት አፍቃሪዎች ውድድሩ በሚካሄድባቸው ቀናት የትራንስፖርት አገልግሎት የተዘጋጀ ሲሆን ሻምፒዮናውን በወጣቶች ስፖርት አካዳሚው ጂምናዚያም በመገኘት በነፃ መከታተል እንደሚቻል ታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኮማንደር ደመላሽ ካሳዬ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ውድድሩን ለማዘጋጀት የበቃችው በመወዳደርያ ስፍራ ጥራት ተቀባይነት በማግኘቷ ነው፡፡

የዞን ሻምፒዮናው የአገሪቱን መልካም ገጽታ የሚገነባ ይሆናል ያሉት ዶ/ር ኮማንደር ደመላሽ በሁለቱም ፆታዎች ያሉትን የኢትዮጵያ የእጅ ኳስ ብሔራዊ ቡድኖች በአፍሪካና በዓለም አቀፍ በየደረጃው የሚኖራቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ ተስፋ ይጠልበታል ብለዋል፡፡ ዓለምአቀፉ የእጅ ኳስ ፌዴሬሸን ከውድድሩ በተያያዘ የዳኝነት እና የአሰልጣኝነት ኮርሶችን እንደሚያዘጋጅ የገለፁት የፌደሬሽኑ ሃላፊዎች በስልጠናው 26 ኢትዮጵያውያን እንደሚሳተፉ አስታውቀዋል፡፡ በኢትዮጵያ የእጅ ኳስ ስፖርት ትኩረት አጥቶ መቆየቱን በጋዜጣዊ መግለጫው ያመለከቱት ዶ/ር ኮማንደር ደመላሽ ፤ የምስራቅ አፍሪካ ሻምፒዮናውን በማዘጋጀት ይህን ሁኔታ ለመቀየር አቅጣጫ መያዙን አስረድተው፤ ከአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የእጅ ኳስ ፌዴሬሽኖች ጋር ያለውን ግንኙነት የምናጠናክርባቸው ስራዎች ይከናወናሉ ብለዋል፡ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ወደፊትም በርካታ ውድድሮችን በማዘጋጀት ወጣቶች በእጅ ኳስ ስፖርት ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ፍላጐት እንዳለውም አስታውቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ሃላፊ የሆኑትና በአፍሪካ ያሉ 10 አገራት በመወከል በኢንተርናሽናል እጅ ኳስ ዳኝነት በመስራት ብቸኛው የሆኑት አቶ ፈረደ ፍትሃነገስት የምስራቅ አፍሪካ ሻምፒዮናው መስተንግዶ ለስፖርቱ ከፍተኛ መነቃቃት የሚፈጥር ብለውታል፡፡ በሁለቱም ፆታዎች ያሉት የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ብሄራዊ ቡድኖች ከሐምሌ 22 ጀምሮ በአራት ኪሎ የስፖርት ማእከል የተሟላ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

አቶ ፈረደ ፍትሃነገስት ፤ በቻሌንጅ ትሮፊው ሁለቱም ብሔራዊ ቡድኖች የዞኑን ሻምፒዮንነት በማሳካት በአፍሪካ ደረጃ የመሳተፍ እድልን በማግኘት ውጤታማ ለመሆን እቅድ አለን ይላሉ። በሁለቱም ፆታዎች ያሉትን ብሔራዊ ቡድኖች ለማቋቋም ሰፊ ትኩረት በመስጠት ሠርተናል ያሉት የቴክኒክ ኃላፊው፣ ሻሸመኔ በተደረገው የፕሮጀክት ውድድር፣ በባህርዳር ለተደረገው የመላው ኢትዮጵያ ጨዋታዎችና ለአዲስ አበባ በሚደረገው የክለቦች ሻምፒዮና ያሉ ስፖርተኞችና ለአዲስ አበባ በሚደረገው የክለቦች ሻምፒዮና ያሉ ስፖርተኞችን ተከታትለን ምልመላ አድርገናል ብለዋል፡፡ በመጀመሪያ ከሐምሌ 12-17 20 ከኦሮሚያ ከአማራ፣ ከትግራይ፣ ከጋምቤላ እና ከአዲስ አበባ “20 ስፖርተኞችን ለሴቶች ብሔራዊ ቡድን መልምለናል ያሉት አቶ ፈረደ፣ የጋምቤላ ክልል ምላሽ አለመስጠቱን ጠቁመው በተካሄደው ምርጫ የሴቶች ቡድኑ ከሐምሌ 17 ጀምሮ ተዘጋጅቷል፡፡ ለወንዶች ብሔራዊ ቡድን ደግሞ ከሐምሌ 17-20 ምርጫ መደረጉን የገለፁት የቴክኒኩ ኃላፊው ከአዲስ አበባ ክለቦች ከትግራይ፣ ከደቡብ፣ ከሶማልያና ከኦሮሚያ ክልል የተውጣጡ ተጨዋቾች መርጠናል፣ ከኦሮሚያ ክልል የተመረጡ ተጨዋቾች መልስ አልሰጡንም የወንዶች ቡድኑ ከሐምሌ 22 ጀምሮ በአራት ኪሎ የስፖርት ማዕከል ልምምድ መስራቱንም ተናግረዋል፡፡ ሁለቱ የወንድና የሴት ብሔራዊ ቡድኖች አንድ ዋና አሰልጣኝና ሌሎች አራት ረዳት አሰልጣኞች ልምምድ ያሰሯቸዋል፡፡ ሁሉም አሰልጣኞች ከሻምፒዮናው በተያያዘ በሚዘጋጀው ስልጠና ተሳታፊ ሲሆን ከአራት ክልሎች ተወጣጥተው የተመረጡ በመሆናቸው በየክልላቸው ስፖርቱን እንዲያስፋፋ ይጠበቃል፡፡

የእጅ ኳስ ስፖርት የሚጀመረው ከ8 ዓመት ጀምሮ ነው ያሉት አቶ ፈረደ፤ በዚህ በኩል የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን የሚያከናውናቸውን መሰረታዊ ተግባራት ለማነቃቃት በመክፈቻው ፕሮግራም ላይ በታዳጊ ህፃናት ስፖርተኞች ትርኢት እናቀርባለን ብለዋል፡፡ የእጅ ኳስ ስፖርትን ከ8-10 ላሉት ታዳጊዎች ስልጠና ለመጀመር ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረግን ነው የሚሉት የቴክኒክ ኃላፊው አቶ ፈረደ፣ በምስራቅ አፍሪካ ሻምፒዮናው በታዳጊዎቹ ትርዒት ራዕያችንን በማንፀባረቅ በቀጣይ አገር አቀፍ ውድድር ለመጀመር ያለንን እቅድ እናስታውቃለን፡፡ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ዶ/ር ኮማንደር ደመላሽ ካሳዬ እንዳስረዱት ከምስራቅ አፍሪካ ሻምፒዮናው አዘጋጅነት በተያያዘ በአህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ፌደሬሽኖች ተጽእኖ ለመፍጠር ፍላጐት አለን ይላሉ፡፡ በተለያዩ የአመራርነት ስፍራዎች ለኢትዮጵያ የሚገባውን ቦታ የምንጠይቅ ይሆናልም ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ባሉት ብሄራዊ ቡድኖች ከአህጉራዊ ውድድሮች መጥፋት የለበትም ያሉት የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት፤ ከዞኑ ሻምፒዮና የተሳካ መስተንግዶ በኋላ በቅርብ ጊዜ ተግባራዊ ለማድረግ ትኩረት የሰጠነው በመላው አፍሪካ ጨዋታዎች የማጣሪያ ውድድር ለመግባት ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ስፖርቱን ለማስፋፋት በዩኒቨርስቲዎች፤ እና በትምህርት ቤቶች ሰፊ እንቅስቃሴዎች ለማድረግ ያቀደ ሲሆን፤ አገር አቀፍ ውድድሮችን በማጠናከር፤ በየክልሎቹ የክለቦችን ብዛት ለማሳደግ፤ በስፖርቱ ሊገኝ የሚችለውን የገቢ ምንጮች በማስፋት ለመስራት ፕሮጀክቶችን ቀርጿል፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ሲቋቋም በእጅ ኳስ ስፖርት ለመስራት ትኩረት አለመሰጠቱ የሚያሳስብ እንደነበር የሚገልፁት የፌደሬሽኑ ሃላፊዎች ሁኔታው ተገቢ አለመሆኑን በመግለፅ ጥያቄ አቅርበን ስልጠናው በአካዳሚው እንዲሰጥ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል፡፡ የእጅ ኳስ ስፖርት በት/ቤቶች፤ በዩኒቨርሲቲዎች፤ በክልሎች እና ክለቦች ሰፊ ተሳትፎ መኖሩን በማገናዘብ የወጣቶች ስፖርት አካዳሚው ለሰጠው አፋጣኝ ምላሽ አድናቆታቸውንም ገልፀዋል፡፡ በአዲስ አበባ እና በሌሎች ክልሎች የእጅ ኳስ ውድድሮችን የሚሳተፉ ክለቦች እየተመናመኑ መምጣታቸውን በተመለከተ በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ጥያቄ የቀረበ ሲሆን የፌደሬሽኑ ሃላፊዎች በሰጡት ምላሽ ውድድሮችን በአገር አቀፍ ደረጃ ለማዘጋጀት ካሉት ፈተናዎች ጋር የተያያዘ ችግር እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ የእጅ ኳስ ፌዴሬሽን በፈለገበት መጠን እንዳይሠራ ዋንኛው ችግር የስፖንሰርሺፕ መንግስታዊ እና የግል ተቋማት በስፖርቱ ለውጥ እና እድገት ሊመጣ እንደሚችል አምነው ሰፊ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የተለያዩ ፕሮጀክቶች እና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች በማዘጋጀት ፌዴሬሽኑ እንደሚሰራ ተገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ የእጅ ኳስ ስፖርተኞች በወቅታዊ የስልጠና ደረጃ እና ሳይንስ ከተሠራባቸው ዓለም አቀፍ ደረጃን የሚያሟሉ ፕሮፌሽኖች ይሆናሉ በማለት ለስፖርት አድማስ አስተያየት የሰጡት ደግሞ የሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ዋና አሰልጣኝ ኢንስትራክተር ሙሉጌታ ግርማ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ያሉ የእጅ ኳስ ስፖርት ሜዳዎች መጠናቸው 40 በ20 ሜትር እንደሆነ የገለፁት ዋና አሰልጣኙ ስፖርቱ ከፍተኛ ፍጥነት ቅልጥፍና የሚጠይቅ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

የኢትዮጵያ ተጨዋቾችን በአሁኑ ጊዜ ያላቸውን ልዩ ብቃት በአሃዛዊ ስሌት ሲያስረዱም አንድ ምርጥ የእጅ ኳስ ስፖርተኛ 30 ሜትር በ4 ሰከንድ ከ1 ሚሊ ማይክሮ ሰኮንድ ይሸፍናል ብለው ብዙዎቹ ወንድ ተጨዋቾቻችን የተጠቀሰውን ርቀት በ4 ሰከንድ ከ30 ሚሊ ማይክሮ ሰኮንድ ይሮጡታል በዚህ አስገራሚ ብቃት ላይ ለ1 ዓመትና ሁለት ዓመት በትኩረት ከተሠራ ፕሮፌሽናል ደረጃ የሚበቁ ስፖርተኞችን በብዛት ማግኘት ይቻላል ብለዋል፡፡ በአውሮፓ ያሉ ፕሮፌሽናል የእጅ ኳስ ስፖርተኞች ተመሳሳይ ርቀትን በአማካይ በ4 ሰኮንድ 60 ሚሊ ማይክሮ ሰኮንድ የሚሸፍኑ በመሆናቸው ለኢትዮጵያውያን ስኬታማነት ማሳያ የሚሆን ነው ያሉት ኢንስትራክተሩ፤ በአውሮፓ የእጅ ኳስ ስፖርት በከፍተኛ ደረጃ በክለቦች ውድድር እንደሚደረግበት በማመልከት ኢትዮጵያውያን ፕሮፌሽናል የእጅ ኳስ ስፖርተኞች ለባርሴሎና፣ ለሪያልማድሪድ እና ለሌሎች የአውሮፓ ክለቦች ማብቃት ይችላል፤ ኬንያ ከ50 በላይ የእጅ ኳስ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች አፍርታለች በማለትም ማስረጃቸውን አስቀምጠዋል፡፡ ኢንስትራክተር ሙሉጌታ ግርማ ኢትዮጵያ በእጅ ኳስ ስፖርት በአፍሪካ ሻምፒዮና፣ በኦሎምፒክ ውድድሮች ለማብቃት ከዞኑ ሻምፒዮና ከሚገኙ ተመክሮዎች ተነስቶ መስራት እንደሚያስፈልግ ያስገነዝባሉ፡፡ ዋና አሰልጣኙ በሰጡት ምክር በመላው አገሪቱ ቁመታቸው ከ1.91 እስከ 2.08 ያላቸው ወጣቶችን በመፈለግ የሚሰራበት ፕሮጀክት በመቅረፅና የስልጠና ባለሙያዎችን በወቅታዊ እውቀትና የብቃት ደረጃ አሰባስቦ በመንቀሳቀስ በሚቀጥሉት 5 ዓመታት ስኬታማ መሆን እንደሚቻል እምነቴ ነው ብለዋል፡፡

                         በተለያዩ ጊዜያት ስለሽንት መቋጠር አለመቻልና የሴቶች የስነተዋልዶ አካላት ጤንነት ግንኙነት አላቸው? ወይንስ የላቸውም? የሚሉ ጥያቄዎች ደርሰውናል፡፡ በዚህ ርእስ ዙሪያ ከደረሱን ጥያቄዎች መካከል ሁለቱን ታነቡዋቸው ዘንድ መርጠናቸዋል፡፡ ሽንቴ አሁንም አሁንም ስለሚመጣብኝ መጸዳጃ ቤት ከሌለበት አካባቢ ጉዳይ ገጥሞኝ ስሔድ እጅግ በጣም እቸገራለሁ፡፡ ብዙውን ጊዜም ባገኘሁበት ቦታ ዘወር ብዬ ከመንገድ ላይ ስለምሸና አለባበሴ ሁሉ እንደልቤ ቁጭ ብድግ ለማለት እንደሚመች ሆኖአል፡፡ ወደሐኪም ቤት ሄጄም ስለጤንነቴ እንዳላማክር ከዚህ ውጭ ሌላ የጤና ችግር አልገጠመኝም፡፡ ስለዚህ ይህ ችግር ከምን የሚመጣ ነው? ስሜን አትግለጹ አንድ ቀን በስራ አጋጣሚ ሽንቴን ከሙሉ ቀን በላይ ሳልሸና ውዬአለሁ፡፡ ከዚያም ወደ አስር ሰአት ገደማ ሲሆን ሽንቴ መጣ፡፡ ለመሽናት ስሞክር ግን ትንሽ ሽንት ብቻ ሸናሁ፡፡ ነገር ግን ሕመም ተሰማኝ፡፡

አሁንም ትንሸ ቆይቶ ሽንቴ መጣሁ ሲል ወደመታጠቢያ ቤት ሔድኩ፡፡ ነገር ግን ከሕመም እና ከማማጥ በስተቀር ሽንት የለም፡፡ በዚህ ሁኔታ ምልልሱ ፈጠን እያለ ሕመሙም እየበዛ እስከ ምሽቱ ሁለት ሰአት ቆየሁ፡፡ ከዚያ በሁዋላ ግን ትንሸ ሽንትና ደም ቅልቅል እየሆነ ህመሙ ተባባሰ፡፡ ወደ ሆስፒታል ስሄድ በየመንገዱ መቆም ነበረብኝ፡፡ ሆስፒታልም ሐኪምጋ እስክቀርብ ድረስ በዚሁ ሁኔታ ሕመሙ ቀጥሎ በጣም አደከመኝ። ሆኖም ግን ታክሜው ድኛለሁ፡፡ የእኔ ጥያቄ... ለመሆኑ ሽንትን በወቅቱ አለመሽናት ለእንደዚህ ያለ ሕመም ይጋብዛልን? ሀና ተፈሪ - ከሳሪስ ከሽንት መቋጠር አለመቻል ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ ችግሮችን ሌሎች ተሳታፊዎችም አድርሰውናል፡፡ ነገር ግን ጥያቄው ...ከሴቶች የስነተዋልዶ አካላት ጋር ተያያዥነት አላቸውን? የሚል እና ሽንትን ቋጥሮ መያዝ ለሕመም ይዳርጋልን? የሚል በመሆኑ ወደ የካቲት 12 ሆስፒታል በማምራት የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስትና የሆስፒታሉ የጽንስና ማህጸን ሕክምና ክፍል ኃላፊን ዶ/ር ብርሀኑ ከበደን ማብራሪያ እንዲሰጡን ለዚህ አምድ ጋብዘናቸዋል፡፡ ዶ/ር ብርሀኑ እንደገለጹት ሽንትን መቋጠር አለመቻል ሲባል ተገቢ እና አስፈላጊ በሆነ ጊዜ መሽናት ሲቻል ነገር ግን ከዚያ ውጪ በማይቆጣጠሩት መንገድ ሽንት ከማምለጥ ደረጃ ሲደርስ ነው፡፡

ጥ/ ሽንትን በተገቢው መንገድ የመያዝ ስርአቱ ምን ይመስላል? መ/ ሽንትን ለተገቢው ጊዜ ተቆጣጥሮ ይዞ አግባብነት ባለው እና ተቀባይነት ባለው መንገድ፣ በፈለጉት ጊዜ ማስወገድ በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ስርአት የሚመራ ነው፡፡ ለምሳሌም ሽንት በተገቢው መንገድ የሚወገደው የታችኛው የሽንት ማለፊያ ቱቦ፣ የሽንት ቱቦውንና ሌሎችንም የመራቢያ አካላት ደግፎ የሚይዙ አካሎች እና በተወሳሰበው የነርቭ ስርአት ጥምረት በሚወሰነው መንገድ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ አንዱ እክል በሚገጥመው ጊዜ የችግሩ ምልክቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ ጥ/ ሴቶች ከስነተዋልዶ አካላት ጋር በተያያዘ የሽንት መቋጠር ችግር ሊደርስባቸው ይችላልን? መ/ ሽንት የመቋጠር ችግር ከሁለት እስከ አራት እጥፍ በሚሆን መልኩ በሴቶች ላይ ጎልቶ ሊታይ ይችላል። ይህም እንግዲህ የሴቶች የሽንት መሽኛ የውጭው አካል አጭር ከመሆኑ የተነሳና እንዲሁም በወሊድና በእርግዝና ጊዜ በስነተዋልዶ አካላት ላይ በሚደርስ ጫና ችግሩ ሊከሰት ይችላል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለሽንት መቋጠር ችግር ምክንያት ይሆናሉ ከሚባሉት ውስጥ እንደ ከፍተኛ ውፍረት፣ እርግዝና፣ ብዙ ልጅ መውለድ፣ ለረጅም ጊዜ ምጥ ማማጥ (ፌስቱላ) በመሳሰሉት ምክንያት በመራቢያ አካላት ላይ በሚደርሱ የተለያዩ ጉዳቶች የተነሳ የችግሩ ተጋላጭነት ይጨምረዋል፡፡ ጥ/ እርግዝና ለችግሩ በምክንያትነት የሚጠቀሰው እንዴት ነው? መ/ በእርግዝና ጊዜ ከሚከሰቱት ፊዚዮሎጂካላዊ ለውጦች መካከል በሆድ አካባቢ የሚፈጠረውን ግፊት ይጨምረዋል፡፡ ይህም በታችኛው የፊኛ አካላት ላይ ተጽእኖ ስለሚያሳድር በቀጥተኛ መንገድ ሽንትን የመቆጣጠር ችግር ሊያስከትል ይችላል፡፡

በሁለተኛም ደረጃ ከመውለድ ስርአቱ ጋር በተያያዘ በተለይም ብዙ የወለዱ ሴቶች በምጥና በተለያየ አጋጣሚ ሰውነታቸው ሊጎዳ ስለሚል ችግሩን ይጨምረዋል። ጥ/ በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት እብጠት ከሽንት ጋር የሚያያዝበት መንገድ አለ? መ/ በእርግዝና ጊዜ የሚታየው እብጠት 80% ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ ይኄውም በእርግዝናው ጊዜ የሚከሰቱት ፊዚዮሎጂካላዊ ለውጦች የሚያመጡት ሲሆን ከደም ግፊት እና ከሌሎች ችግሮች ጋር ካልተያያዘ በስተቀር ብዙ ጊዜ እንደችግር አይታይም፡፡ አንዳንዴ ግን ከኩላሊት እና ከሌሎች የውስጥ አካላት ችግሮች ጋር ሲገናኝ እና እብጠቱ ከእግር አልፎ ወደእጅ እንዲሁም በፊት ላይ የሚታይ ከሆነ ክትትል ያስፈልገዋል፡፡ ይሁን እንጂ በእርግዝና ጊዜ የሚታየው የሰውነት እብጠት ሽንትን ከመቋጠር ወይንም ካለመቆጣጠር ጋር የሚገናኝ አይደለም፡፡ ጥ/ በተጠቀሱት ምክንያቶች ሳቢያ የሚደርሰው የጤንነት ችግር ምን ይመስላል? መ/ የታችኛው የሽንት ቧንቡዋ እና ሌሎች የመራቢያ አካላትን በማርገብ እንዲሁም ደግሞ የረጅም ጊዜ ምጥ በሚኖርበት ጊዜ በዚያ አካባቢ ያሉ አካላት የደም ዝውውር በማጣታቸው የተነሳ ከተወሰነ ጊዜ በሁዋላ ቀዳዳ መፍጠር፣ በእድሜ ምክንያት የወር አበባ መቆም ጋር ተያይዞ በሚፈጠረው የኢስትሮጂን የተባለው ንጥረ ነገር እጥረት የተነሳ መሳሳቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ በስነተዋልዶ አካላት አካባቢ የሚደረጉ ኦፕራሲዮኖች፣ የጨረር ሕክምናዎች ለሽንት መቋጠር ችግር ሊያጋልጡ ይችላሉ፡፡ ጥ/ ሽንትን የመቆጣጠር ችግር ምን ያህል አስከፊ ነው? መ/ ችግሮቹ ሲከሰቱ የሚሰጠው ትኩረት ከቦታ ቦታ እንደየሀገሮቹ የእድገት ደረጃ እና የአኑዋኑዋር ሁኔታ የተለያየ ቢሆንም ከህክምናው ወይንም እንደበሽታ ከመታየቱ ውጪ በሰዎች የአኑዋኑዋር ዘይቤ ላይ ያለው አስተዋጽኦ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡

ሰዎች በደረሰባቸው ችግር ይጨነቃሉ፣ ያፍራሉ፣ ድብርት ይገጥማቸዋል፣ ከሰዎች ጋር ለመገናኘት የማይቻልባቸው ሁኔታዎች ያጋጥማሉ፡፡ ስለዚህም ችግሩ ከገጠማቸው ሰዎች መካከል ወደሕክምና የሚመጡት ከግማሽ በታች እንደሚሆኑ ይገመታል፡፡ የዚህም ምክንያት ችግሩን ለሰው ለማማከር ከማፈር ወይንም ደግሞ የህክምና እርዳታ አለው ብለው አለማሰባቸው ሊሆን ይችላል። ብዙዎች በቤታቸው ችግራቸውን አፍነው በመያዝ ቶሎ ቶሎ ሽንት ቤት በመሄድ ወይንም ከስራ በመቅረት እራሳቸውን ለማስታመም ስለሚሞክሩ ይህም በቤተሰብ፣ በህብረተሰብ እንዲሁም በአገር ላይ ችግር ማስከተሉ ስለማይቀር ኪሳራ ያመጣል፡፡ ስለዚህም በአግባቡ የህክምና እርዳታ ሊያገኝ የሚገባው የጤና ችግር ነው፡፡ ጥ/ ሕክምናው ምን አይነት ነው? መ/ ከታመሙት መካከል ከግማሽ በታች የሆኑት ወደሕክምና ይመጣሉ ቢባልም የመጡትን በአግባቡ በህክምናው የመርዳት አሰራር አለ፡፡ የሽንት መቆጣጠር ችግር ሊከሰትባቸው የሚችሉ ምክንያቶችና በአካል ላይ የሚታየው ሕመም ከላይ ተገልጾአል፡፡ ስለሆነም የአካል መላላት ወይንም መርገብ የመሳሰሉት ችግሮች ሲከሰቱ በሳል ወይንም በሳቅ ጊዜ ሽንት ሊያመልጥ ይችላል፡፡ እንዲሁም የሽንት አወራረድ ስርአቱን በማየት ሽንት ማምለጡ አልፎ አልፎ ነው ወይንስ በተከታታይ ነው የሚለውን ተገቢውን ጥያቄዎች በመጠየቅ አስፈላጊውን ምርመራ በማድረግ እንዲሁም በተሸሻሉና ችግሩን ሊለዩ በሚችሉ የምርመራ መሳሪያዎች በመታገዝ እንደአስፈላጊነቱ አስፈላጊው ሕክምና ይሰጣል፡፡

ጥ/ የሽንት የመቆጣጠር ችግር የደረሰባቸው ሴቶች እራሳቸውን ሊረዱ የሚችሉበት እድል ይኖራል? መ/ የደረሰው የጤና ችግር ቀለል ያለ ከሆነ ለምሳሌም የታችኛው ሽንት መውረጃ አካላት አካባቢ ያለ የሰውነት ክፍል መርገብ የደረሰበት መሆኑ በሕክምና ሲረጋገጥ ከሕክምና ባለሙያው በሚሰጠው ምክር መሰረት የጡንቻ አካሎችን ለማጠንከር የሚሰሩ የሰውነት ማጠንከሪያዎች አሉ፡፡ ሰውነትን ጭምቅ አድርጎ እየያዙ በመልቀቅ ጊዜ ሰጥቶ በቀን ውስጥ ሶስት አራት በመስራት ሴቶቹ መጠነኛ የሆነ እርዳታን ለእራሳቸው ማድረግ ይችላሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከሆርሞን እጥረት ጋር የተያያዘ ከሆነ ኢስትሮጂን የተባለውን ሆርሞን በመቀባት ወይንም በኪኒን መልክ በመውሰድ ሰውነት ያጣውን ንጥረ ነገር በመተካት ችግሩን ማቃለል ይቻላል፡፡ ጥ/ ሽንትን ሳይሸኑ ቋጥሮ በመያዝ ምክንያት ሕመሙ ሊከሰት ይችላልን? መ/ ሽንት በሚቋጠርበት ጊዜ የሚደርሰው የፊኛ መወጠር በሁዋላ ላይ ለሚከሰተው ሽንትን በተገቢው መንገድ የማስወገድ ችግር እንደምክንያት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ስለዚህም ሽንትን ሳይሸኑ ለረጅም ጊዜ መያዝ ሽንት እንዲረጋ ስለሚያደርግ እና የሽንት ፊኛ ኢንፌክሽን ስለሚያስከትል በጊዜያዊ መልክም ቢሆን ለሽንት መቋጠር ችግር መንስኤ ይሆናል ሊባል ይችላል፡፡

Published in ላንተና ላንቺ

ርዕስ- ጳውሎስ ኞኞ (1926-1984)፣
የገፅ ብዛት - ከፎቶና ማጣቀሻ ጽሑፎች ዝርዝር ጋር 308፣
የሽፋን ዋጋ - 84 ብር (24 ዶላር)፣
የህትመት ዘመን - 2006 ዓ.ም
ህትመት - አርቲስቲክ ማተሚያ ድርጅት
ጸሐፊ - ደረጀ ትዕዛዙ
በዘመናችን ግለታሪኮችና ታሪኮች በብዛት ባይሆንም በተሻለ መጠን ለህትመት እየበቁ ናቸው፣ ይህ መልካም ጅምር መጠናከር ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም ዓለማችንን የቀየሩዋት ባለ ልዩ አዕምሮ ግለሰቦች ናቸው፤ በእነሱ ጥረትና የድካም ፍሬ ድምሩ ህዝብ ተጠቃሚ ሆኗል፤ ይሆናልም፡፡ እንኳንስ ተፈጥሮ አድልታ ባለ ምጡቅ አዕምሮ ያደረገቻቸው ግለሰቦች ይቅሩና የኔቢጤው በረንዳ አዳሪ ሁሉ ቀርቦ የሚያነበው ቢያገኝ ታላቅ መጽሐፍ ነው፤ ታላቅ መረጃ በውስጡ ይኖራል፡፡
ከነገስታትና ልኡላን ዜና መዋዕሎች በቀር እብዛም ያልተለመደ የነበረው የግለሰቦች ታሪክ በቤተሰቦቻቸው፣ ወይም መልካም ፈቃዱና ችሎታው ባላቸው ግለሰቦች አማካይነት እየተጻፈ ልምዳቸውን እንድንካፈል የላቀ ድርሻ እየተወጡ ናቸው፡፡ በቅርቡ ታትሞ ገበያ ላይ የዋለውና በጳውሎስ ኞኞ የህይወትና ሥራ ታሪክ ላይ የሚያጠነጥነው መጽሐፍም ከእነዚህ የግለሰብ ታሪኮች የሚመደብ ነው፡፡
በዘጠኝ ምዕራፎች የተከፋፈለው የ“ጳውሎስ ኞኞ” መጽሐፍ፤ የተለያዩ ፎቶግራፎችንና ውሱን ሰነዶችንም አካትቷል፡፡ ስለጳውሎስ ልደት፣ ዕድገት፣ ትምህርት፣ ሥራና ባህርይ የሚያትተው ይህ መፅሀፍ፤ ከጳውሎስ ጋር ባላንጣ ስለነበሩት የወቅቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር ደጃዝማች ግርማቸው ተክለሐዋርያትም የሚያካፍለን ቁም ነገር አለ፡፡
ጳውሎስ ያልሞከረው ሥራ የለም ማለት ይቻላል፤ ግለሰብ ሱቅ ውስጥ ተቀጥሮ መስራት የጀመረው ገና በልጅነት ዕድሜው ሲሆን ትምህርቱን ከአራተኛ ክፍል ያቋረጠውም በድህነት ምክንያት ነው፡፡ (ገፅ 16) ከግሪካዊው ኞኞ እና ከኢትዮጵያዊቷ ወ/ሮ ትበልጫለሽ ቁልቢ ገብርኤል አካባቢ የተወለደው ጳውሎስ፤ የልጅነት ህይወቱ የተመሰቃቀለ ነበር፡፡ እናቱ ፍጹም ድሃ በመሆናቸው እንደ እመጫት ድመት በየቦታው ይዘውት ስለሚዞሩ በትምህርቱ ላይ ጫና መፈጠሩ የግድ ነበር፡፡
እናቱ ወ/ሮ ትበልጫለሽ ከሸዋ ወደ ሐረርጌ የሄዱ ምስኪን በመሆናቸው የረባ ዘመድ አልነበራቸውም፤ እንኳን የእናቱ ዘመዶች ግሪካዊ ነጋዴ አባቱ እንኳ ልጁን ዞር ብሎ የማየት ዕድሉ አልነበረውም፡፡ ስለዚህ ጳውሎስ ድህነትን ገና በጨቅላ ዕድሜው ነው መልመድ የጀመረው። ድሃ ነበር፤ መናጢ ድሃ፡፡ ትምህርቱን ከአራተኛ ክፍል አቋርጦ እናቱን ለመደጎም፣ ራሱንም ለመርዳት ከአንድ ግለሰብ ሱቅ ተቀጠረ፡፡
ተቀጥሮ መስራት አላዋጣው ሲል ፓስቲ እያዞረ መሸጥ ጀመረ፡፡ ከሌሎች የተለየ ለመሆንም እንቁላል ይቀቅልና በተለያዩ ቀለማት አሸብርቆ፣ በባቡርና በመንገድ በመዞር እየሸጠ የተሻለ  ገቢ ማግኘት ቻለ፡፡ ከሁሉም የሚገርመው ግን አንበጣ እየሰበሰበ ለውጭ ዜጎች በመሸጥ ገቢ ማግኘቱ ነው፡፡ ጋዜጣ እያዞረ ይሸጣል፡፡ የተባይ ማባረሪያ ጭራ በመሸጥም እናቱን ይደጉም ነበር፡፡ ሎሚ እየጨመቀና በቀለም እየበጠበጠ ስኳር በመጨመር “ሸርፔቴ” በሚል ስያሜ ይሸጥ እንደነበር ታሪኩ ያወሳል፡፡
ጳውሎስ ሰዓሊም ነበር፤ የመላእክት፣ የጻድቃንና የሰማዕታትን ስዕሎች እየሳለ በየቡና ቤቱ በማዞር በሁለት ብር ሲሸጥ፤ የተለያዩ አርበኞችን ምስል በመሳልም ደህና ገቢ ያገኝ ነበር፡፡ ጳውሎስ ገና በልጅነት ዕድሜው ድህነት ቢፈትነውም እጁን አልሰጠም፤ አንዱን ሥራ ይሞክርና ተቀናቃኝ ሲበዛበት ሌላ ነገር ይፈጥራል፤  ያ ሲለመድበትም ወደ ሌላው ይዞራል፡፡ ሆኖም ሥዕሉን ወይም ዕንቁላሉን ወይም ፓስቲውንም ሆነ አንበጣውን ሲያዞር የጋዜጣ ብጣሽ ካገኘ በተአምር ጥሏት አያልፍም፤ ሱቅ ታዝዞ ሄዶ የገዛትን ቡናም ሆነች ስኳር ለእናቱ ካደረሰ በኋላ ዕቃዋ የተጠቀለለችበትን የጋዜጣ ብጣሽ ወይም ወረቀት ያነሳና ያነብባል፡፡ በንባብ የተለከፈው ገና በልጅነቱ ነው፡፡
የእንቁላሉን፣ የፓስቲውን፣ የአንበጣውን፣ የጭራውን፣ የሎሚ ጭማቂውን “ሸርፔቴ” ንግድ፣ ወይም የስዕሉን ንግድ እያፈራራቀ ሲያስሄድ ከቆየ በኋላ፣ በእርሻ ሚኒስቴር ውስጥ የእንስሳት መርፌ ወጊ ሆኖ በስምንት ብር የወር ደሞዝ ተቀጠረ፡፡ ለሶስት ዓመታትም በጨርጨር አውራጃ እንስሳትን መርፌ እየወጋ ሲያገለግል ቆየ፡፡ በእንስሳት ላይ ተግባራዊ ያደረገውን መርፌ የመውጋት ልምድ በመጠቀም “ደደር” ከተባለ ቦታ በአርባ ብር ደሞዝ ተቀጥሮ ሰዎችን መርፌ ለመውጋት ከሚሲዮኖች ጋር ይሰራ ጀመር፡፡
በ1964 ዓ.ም ደግሞ ዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል አውጥቶት የነበረውን የድሬሰርነት ውድድር አልፎ ወደ አዲስ አበባ መጣ፡፡ ደሞዙም ሰማንያ ብር ገባለትና ተደሰተ፡፡ በሂሳብና በጽሑፍ ሙያ ጭምር ሆስፒታሉን በማገልገልም ተወዳጅ ሆነ፡፡ ጋዜጠኝነትን በእውኑም ሆነ በህልሙ አስቦት አያውቅም፤ ግን አንድ አጋጣሚ ድንገት ገፈተረውና የዕድሜ ልክ ቁራኛ አደረገው፡፡
ጋዜጠኛ ለመሆን የበቃበት ምክንያት አስገራሚ ነው፤ ዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል እያለ እሱና ጓደኞቹ በብድር ልብስ ይሰፋላቸዋል፡፡ የወሰዱትን ብድር በስድስት ወር ክፈሉ ሲባሉ ወሽመጣቸው ተበጠሰ፤ ከዚያ “ሳንፈልግ አበድረውን ገንዘባችንን በሉን በቃሪያ ነው የምንዘልቀው” የሚል ይዘት ያለው ጽሑፍ “ለማን አቤት ይባላል?” በሚል ርዕስ ጻፈና ለኤርትራ ድምፅ ጋዜጣ ላከው፡፡ ጋዜጣውም ጽሑፉን ጥር 4 ቀን 1948 ዓ.ም ይዞት ወጣ፤ ጳውሎስ ደስ አለው፡፡
በዚህ ሁኔታ ላይ እያለ እዚያው ምኒሊክ ሆስፒታል ውስጥ ከምትሰራና “ፈለቀች” ከምትባል ቆንጆ ጋር በፍቅር ይወድቃል፡፡ ፍቅሩን የሚገልፅለት ግጥም ጽፎ ለጋዜጣ ላከው፤ እሱም እንዳለ ወጣለትና ፈነደቀ፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ ጽሑፍ አዘነበለ፤ ትክክለኛ መክሊቱንም አገኘ፡፡
ጳውሎስ የጋዜጠኝነት ስራውን “ሀ” ብሎ የጀመረው በድምፅ ጋዜጣ ነው፡፡ ለዚያ ያበቁት ደግሞ በወቅቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር የነበሩት አቶ መኮንን ኃብተወልድ ናቸው፡፡ ጋዜጣዋን በህዝብ ዘንድ ተወዳጅ በማድረጉም ከንጉሠ ነገሥቱ የጽህፈት መኪና (ታይፕራይተር) ተሸልሟል፡፡ ይህ ሽልማት ግን መኮንን ኃብተወልድን በተኳቸው የማስታወቂያ ሚኒስትሩ ዘንድ አልተወደደለትም፡፡
አዲሱ ሚኒስትር ደጃዝማች ግርማቸው ተክለሐዋርያት ሲሆኑ ጠባቸው እስከ መጨረሻ ዘልቋል፡፡ የጳውሎሷ “ድምፅ” ጋዜጣ በህዝብ ዘንድ እጅግ ተወዳጅ የመሆኗን ያህል በመንግስታዊው “አዲስ ዘመን” ጋዜጣ ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደር ጀመረች፡፡ ጳውሎስ ጋዜጣ አዟሪዎችን ሳይቀር የደንብ ልብስ አዘጋጅቶ በማሰራት ጋዜጣዋን ታዋቂ አደረጋት፡፡
ሆኖም የደንብ ልብስ እየለበሱ “ድምፅ” ጋዜጣን የሚያዞሩ ሁሉ እየተለቀሙ እስር ቤት እንዲታጎሩ ደጃዝማች ግርማቸው ለፖሊስ ትዕዛዝ በመስጠታቸው፣ ጳውሎስ በጣም ተበሳጨ፤ የኋላ ኋላ እሱም አልቀረለት፡፡ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ዋለና በስንት መከራ በዋስ ተለቀቀ።
ፍቅሩ ኪዳኔ፣ መሥፍን ወልደማርያም፣ መርቆሬዎስ፣ አጥናፍሰገድ ይልማ፣ አሳምነው ገብረወልድ፣ ከፍያለው ማሞ፣ ተፈራ ወልድአገኘሁ፣ ነጋ ወልደሥላሴ፣ ሰለሞን ተሰማ፣ ትዕዛዙ ሳህሉ፣ ፍቅረሥላሴ ወልደሐና፣ ማሞ ውድነህና ሌሎችም ዕውቅ ጋዜጠኞችና ጸሐፍት በ“ድምፅ” ጋዜጣ ላይ ይሳተፉ ነበር፡፡
ጳውሎስ ከ “ድምፅ” ጋዜጣ ወደያኔው “የወሬ ምንጭ” አሁን “ዜና አገልግሎት”፣ አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ በመጨረሻም ኢትዮጵያ ሬዲዮ ተዘዋውሮ አገሩን አገልግሏል፡፡ ዝነኛ የነበረው ግን መጀመሪያ በ“ድምፅ” ጋዜጣ በኋላም በ “አዲስ ዘመን” ጋዜጣ ላይ ይጽፋቸው በነበሩ ጽሑፎቹ ነው፡፡ ጳውሎስ ያለመታከት ይጽፋል፤ ያለአንዳች ፍርሃት ይተቻል፤ እውነትን የህይወቱ መርህ ያደርጋል፡፡ በዚህ የተነሳ በርካታ ምስጋና፣ ጥቂት የማይባልም ወቀሳና ዘለፋ፣ ግፋ ሲልም ክስና በየፖሊስ ጣቢያው መጎተት ይደርስበት ነበር፡፡
“የተማርሁት ከነቃፊዎቼ ትችት ነው” የሚለው ጳውሎስ፤ ራሱን በራሱ በማስተማር፣ በንባብ ራሱን የተዋጣለት ጋዜጠኛ አድርጎ የፈጠረ ሰው ነው፡፡ ካላነበበ ያመዋል፤ ካልፃፈ እንደ ባለ ዛር ያቅበጠብጠዋል፡፡ ጠባዩ ሁሉ ይቀያየራል፡፡
“አንድ ጥያቄ አለኝ” በሚል ርዕስ ሥር ለሚመጡለት እጅግ በርካታ ጥያቄዎች በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ተገቢውን መልስ በመስጠት ዝናን ያተረፈው ጳውሎስ፤ ጋዜጠኛ ብቻ ሳይሆን የታሪክ፣ የልብወለድ እና የግጥም ጸሐፊም ነበር፡፡ ከአራተኛ ክፍል ትምህርቱን አቋርጦ ይህን ሁሉ እውቀት ያገኘው ከንባብ ነው፡፡
በትዳር በኩል ጳውሎስ ብዙ ፈተናዎችን አይቷል፤ አራት ሴቶችን በተራ አፍቅሮ አልተሳካለትም፡፡ “ማሚቴ፣ እታፈራሁ፣ ፈለቀች፣ የሹምነሽ” የተባሉ ቆነጃጅትን በየተራ አፍቅሮ ከትዳር ወግ ሳይደርስ ቆይቶ ነበር፡፡ ከጊዜ በኋላ ግን የቤቱ አከራይ ልጅ ከነበረችና “አዳነች” ከምትባል ቆንጆ ጋር የሰመረ ትዳር መሥርቶ እስከ መጨረሻው መዝለቅ ችሏል፡፡ አዳነችን የወደዳት አባቷ ሞተው ደረቷን ገልጣ ስታለቅስ አይቶ ነው፡፡
በደረቷ ፍቅር ወደቀ፤ አገባት፣ እስከ መጨረሻውም አብረው ዘለቁ። ጳውሎስ በሐይማኖት ረገድ በአባልነት የተሰለፈበት ቡድን አልነበረም፣ የእግዚአብሔርን ስም የሚጠራ ሁሉ ትክክል ነው ብሎ ስለሚያምን፣ ኦርቶዶክስም፣ ፕሮቴስታንትም፣ ካቶሊክም፣ ሙስሊምም፣ ባህላዊ ሃይማተኛም ሆኖ ህይወቱን ገፍቷል፡፡ ህዝብ የሚያምነው ሁሉ ትክክል ነው የሚል አቋም የነበረው ይመስላል፡፡
በማህበራዊ ህይወቱ ታላላቅ ተግባራትን በማከናወን የሚታወቀው ጳውሎስ፤ የጋዜጠኞችን ማህበር አይወደውም ነበር፤ እንዲያውም “ማኅበሩ ለአረቄ የተቋቋመ ነው፤ ሙያችንን የማያዳብር፣ የጋዜጠኞች ሙያ ምን እንደሆነ የማያውቅ… እንዲህ አይነት ደደብ ማኅበር እኔም ትቸዋለሁ” ብሎ እስከመናገር የደረሰበት አጋጣሚ አለ (ገፅ 2004)፡፡
ለእንስሳት ልዩ ፍቅር የነበረው ጳውሎስ፤ በህዝብ እንደተወደደና እንደ ተከበረ የዘለቀ ምርጥ ጋዜጠኛ መሆኑን ጓደኞቹና የሥራ ባልደረቦቹ ሁሉ የመሰከሩለት ዕውነት ቢሆንም ቁጣው አፍንጫው ስር ነበር፤ ግን ወዲያው ይረሳል፤ ቂም አያውቅም፡፡
በአጭሩ ጳውሎስ ይህን ይመስላል፣ እንደ ደረጀ ትዕዛዙ መጽሀፍ፡፡ መጽሐፉ በዚህ ደረጃ መገኘቱ ጥሩ ነው፡፡ ሆኖም የጳውሎስ ሥራ፣ ማህበራዊ ህይወትና ቤተሰባዊ መዋቅር ይህ ብቻ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡
ደረጀ የጳውሎስን መጽሐፍ “ግለታሪክ” ነው ሲልም ደጋግሞ ጽፏል፡፡ ይህ ስህተት ነው፤ መጽሀፉ የጳውሎስን ታሪክ የሚያሳይ (biography) እንጂ የደረጀ ግለታሪክ (autobiography) አይደለም፡፡
ደረጀ ስለራሱ የህይወት ታሪክ ቢጽፍ ነበር “ግለታሪክ” የሚሆነው፡፡ አለዚያም ልክ እንደ ፊት አውራሪ ተክለሐዋርያት ተክለማርያም ወይም እንደ ራስ እምሩ ኃይለሥላሴ ወይም እንደ ተመስገን ገብሬ፣ ጳውሎስም የራሱን ታሪክ ጽፎ ቢሆን ኖሮ “ግለታሪክ” ሊባል ይችል ነበር፡፡ ግለታሪክ ማለት የራስን ታሪክ በራስ መጻፍ ማለት ነው፡፡
መጽሐፉ የመዋቅር ችግርም አለበት፤ ለምሳሌ ጡረታ መውጣቱን ሲነግረን ይቆይና ስለትዳሩ ሊተርክልን ሞክሯል፤ በደጃዝማች ግርማቸውና በእርሱ መካከል ስለነበረው ዘላቂ ፍትጊያም ወዲያና ወዲህ እየተወራጨ ነው የሚነግረን፡፡ በቋንቋ ረገድ እንከን የለሽ ነው ባይባልም ሊነበብ የሚችል መጽሐፍ ነው፡፡ አልፎ አልፎም ቢሆን የፊደል ግድፈት ስላለበት ድጋሚ በሚታተምበት ጊዜ ግድፈቶቹ ሊታረሙ ይገባል ብዬ አምናለሁ፡፡
ከሁሉም በላይ ግን የጳውሎስ ህይወት እንቆቅልሽ  ነው የሚባለው የቤተሰቡ ሁኔታ ነው፤ አባቱ ኞኞ መርከበኛ እንደነበር ተወስቷል፡፡ ግን ቁልቢ ድረስ የሄደበት ምክንያት፣ ለምን ሳይመለስና ልጁን ሳይጠይቅ እንደቀረ፣ “ሐዋርያው” የሚባለውና በስሙ የሚጠራው ወጣት “ልጁ አይደለም” የሚሉ ወገኖችም ስላሉ፣ ጥርት ብሎ ቢገለጥ መልካም ነበር የሚል እምነት አለኝ፡፡ በተረፈ የጳውሎስ መልእክት “ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች ሆይ! እንዲሁም መላው የሃገሬ ህዝብ! እባካችሁ አንብቡ!!” የሚል ነው፡፡  ጳውሎስን ዳግም የፈጠረው ንባብ ነውና!

Published in ጥበብ

   “ኒሂሊዝም” (Nihilism) በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ በምድረ አውሮፓ የተነሳ ርዕዮት ሲሆን ቃሉን ለመጀመሪያ ጊዜ የተገለገለው ጀርመናዊው ፈላስፋ ፍሬድሪክ ሄኔሪክ ጃኮቢ (1743-1819) ነው፡፡ ኒሂሊዝም እንደ የሚገባበት አውድ እና ዲሲፕሊን የተለያዩ መልኮች ቢኖሩትም አስኳሉ “ክህደት” ነው፡፡ ሃይማኖት ቢሉ እምነት፣ ባህል ቢሉ እውቀት፣ ህግ ቢሉ መተዳደሪያ ደንብ፣ ስነ ምግባር ቢሉ ስሜት… ከነጓዛቸው በኒሂሊዝም ይገፋሉ፤ ይካዳሉም፡፡ እውቁ አሜሪካዊው ፈላስፋና ደራሲ ኮርኔል ዌስት ኒሂሊዝምን አስመልክቶ እንዲህ ይላል:- “Nihilism is a natural consequence of a culture (or civilization) ruled and regulated by categories that mask manipulation, mastery and domination of peoples and nature.”  
የሰው ልጅ በማህበር ሲኖር ህልውናውን የሚያስጠብቅባቸው፣ ባህሉን የሚያስከብርባቸውና ለትውልድ የሚያስተላልፍባቸው፣ እውቀቱን የሚሰፍርባቸው፣ ስሜቱን የሚገልጽባቸውና ስነ ምግባሩን የሚተረጉምባቸው እሴቶች አሉት፡፡ እነዚህ እሴቶች የሰው ልጅ ራሱ ፈጥሮአቸው በብዙም ሆነ በጥቂቱ ተገዝቶ የሚኖርባቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡ አንድ ማህበረሰብ እንደ ማህበር ራሱን የሚገልጥበትና ህላዌውን የሚያዘልቅበት ባህል አለው፡፡ ባህል ለተፈጥሮአዊ ጉዳዮች የሚሰጥ “ምላሽ” (expression) ነው፡፡ እምነት፣ ሃይማኖት፣ እውቀት፣ ሞራል፣ ልማድ፣ ህግ/መተዳደሪያ ደንብ፣ ኪነ-ጥበብ፣ ምርትና ማምረቻ መሳሪያ፣ አልባሳት፣ ወዘተ. . . የባህል ዘርፎች ናቸው፡፡ ተፈጥሮአዊ ባለመሆኑ አይነቱ ይለያይ እንጂ በየትኛውም ማህበረሰብ ውስጥ ባህል አለ። ማህበረሰቡ ለዘርፎቹ ያለው አመለካከት ቢለያይም ለእሴቶቹ እውቅናን ይሰጣል፡፡ አስፈላጊነታቸውንም ያምናል፡፡
ኒሂሊዝም እነዚህን ሰዋዊ እሴቶች ይክዳል፤ አላስፈላጊነታቸውንም ይሰብካል፡፡ መሰረት የሌላቸውና አንዳችም ጥቅም የማይሰጡ መሆናቸውን በመግለጽ በሰው ልጅ ህላዌ ውስጥ ያላቸውን ህልውና ይገዳደራል። በዚህ ጽሑፍ ኒሂሊዝም፣ የስብሐት ገብረ እግዚአብሔር ድርሰት በሆነው “ኮተት” ላይ እንደምን አቢይ ጭብጥ ሆኖ እንደቀረበ ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡ አስረጂዬም ድርሰቱ የማህበረሰብን የተከበሩ “ነባር እሴቶችን እና እሴቶቹ የተመሰረቱባቸውን የሃይማኖት፣ የፖለቲካ እና የስነ ምግባር መርሆዎች የሚቀናቀን”፣ የሚክድና የሚኮንን መሆኑ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ስነ ፅሑፍ ውስጥ አቢይ ጭብጡን ኒሂሊዝም ያደረገ ሌላ ድርሰት አላጋጠመኝም። የማህበረሰቡ እሴቶችና የእሴቶቹ መርሆዎች የሚያራምዱትን አንዳንድ አስተሳሰቦች በመቃወም (በተለይ ሊሻሻሉ ይገባል በማለት) በሳሉአቸው ገፀባህሪያት አማካይነት የሚሞግቱ በርካታ ድርሰቶች አሉ፡፡ እንደ አስረጂም “ፍቅር እስከ መቃብር”- በጉዱ ካሳ፣ “ሀዲስ”- በሀዲስ፣ “አርአያ”- በአርአያ እና “ሚክሎል”- በገልገሎ አማካይነት ያቀነቀናቸውን የለውጥ አስተሳሰቦች መጥቀስ ይቻላል፡፡ ሆኖም በእነዚህ ድርሰቶች የተነሱትና በእሴቶቹ ላይ የተደረጉት ትችቶች፣ እሴቶቹ እና የእሴቶቹ መሰረቶችን መኖርና አስፈላጊነት የሚቃወሙና የሚክዱ ሳይሆኑ እሴቶቹ እንዲታረሙና እንዲሻሻሉ የሚፈልጉ ናቸው፡፡ በመሆኑም የስብሐት “ኮተት” ኒሂሊዚምን በማቀንቀን፣ የሰው ልጅ ነባር እሴቶችና የእሴቶቹን መሰረቶች ህልውና በመቃወምና በመተቸት፣ አላስፈላጊነታቸውንም (“ኮተት” ናቸው በማለት) በመስበክ ብቸኛ የአማርኛ ልቦለድ ድርሰት ይመስለኛል፡፡ (ልብ በሉ ነው አላልኩም፡፡)
በአብዛኛው ማህበረሰብ ውስጥ (አይነቱና መጠኑ ይለያይ እንጂ) ልብስ ለሰው ልጅ መጠቀሚያው ነው፡፡ ራሱን ከብርድ እና ከፀሐይ ይከላከልበታል፤ ያጌጥበታል። የተለያዩ ማህበራዊ ክዋኔዎችንም ይከውንበታል፡፡ የሰው ልጅ ራሱን ከጠላት፣ አካሉን ከብርድ እና ከፀሐይ ለመከላከል፣ እየሰለጠነ ሲመጣም በምቾት ለመኖርና ለሌሎች ፋይዳዎች ሲል ጎጆ ይቀልሳል፡፡ እንደ ኑሮ አቅሙም የቤቱን ደረጃና ቁጥር ይወስናል፡፡ ይህ ጅማሬ ስልጣኔውን ተከትሎ አሁን ያለው የስነ- ህንፃ ጥበብ ደረጃ ላይ ደርሶአል፡፡ አይነቱና መጠኑ ይለያይ እንጂ የሰው ልጅ ውሎ መግቢያ ጎጆ አለው፡፡ እነዚህ እሴቶች አይነታቸውና መጠናቸው ከማህበረሰብ ማህበረሰብ ቢለያይም አይቀሬነታቸው አያጠያይቅም፡፡ የሰው ልጅ እንደ ግለሰብም ሆነ በማህበር አምኖ የተቀበላቸውና የሚጠብቃቸው፣ በጊዜ ሂደትም ስልጣኔውን ተከትሎ ያሻሻላቸውና የሚያሻሽላቸው እሴቶቹ ናቸው፡፡
በ“ኮተት” የእነዚህ እሴቶች አስፈላጊነት፣ ጠቃሚነትና የግድነት ይካዳል፡፡ አልባሳት፣ ቤቶች እና ቁሳቁስ/መገልገያ መሳሪያዎች በድርሰቱ ውስጥ አላስፈላጊ “ኮተቶች” ናቸው፡፡ የአቶ አልአዛር ውሻ ኮምቡጠር ኒሂሊዝምን የሚሰብክ/የሚያራምድ ገፀባህሪ ነው፡፡
“. . .የልብሳችሁ ብዛት! ሙታንታ- ካናቴራ- ሸሚዝ- ሹራብ- ኮት- ካፖርት- ባርኔጣ- ካልሲ. . . አልጋ ልብስ- ፎጣ! ኧረ ወዲያ! ኮተታም ዘር!. . .
. . .ደሞ የቤታችሁ ጣጣስ? ማድቤት- ምግብ ቤት- እንግዳ ቤት- ሽንት ቤት- እቃ ቤት- ወምበር- ጠረጴዛ- ሶፋ- ምንጣፍ- አልጋ- ቁምሳጥን- አግድም ሳጥን! ሌላ ኮተት ዝባዝንኪ ግሳንግስ!. . .”(166)
ሃይማኖት(Religion) ሰዋዊ እሴቶች ከሚመሰረቱባቸው መርሆዎች አንዱ ነው፡፡ በስሩም የሚደረጉ እና የማይደረጉ ተብለው የተቀመጡ በርካታ “ውሳኔዎችን” ይይዛል፡፡ ተከታዮቹም/ምዕመናኑም ለእነዚህ ስርዓቶች እንዲታመኑ የግድ ይላል፡፡ ሃይማኖት በሰው ልጅ እውቀት(intellectual)፣ ስሜት(emotion) እና ስነ ምግባር(moral) ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ አለው። በመሆኑም ሰው ለሃይማኖቱ የሚሰጠው ቦታ እጅጉን ክቡር ምንአልባትም አይነኬ ነው፡፡ አንዱ የደስታ መግለጫ ሌላው የሀዘን ማሳያ ቢሆኑም ሠርግ እና ተዝካርም በማህበረሰብ ውስጥ ያላቸው ቦታ፣ ቅቡልነት እና ተፈጻሚነት (በተለይ በእኛ ሀገር) እጅጉን ትልቅ ነው፡፡
ህጎች/መተዳደሪያ ደንቦች(codes) የሰው ልጅ እንደግለሰብ ገደብ አልባ ፍላጎቱን(desire) የሚገራባቸው፤ እንደማህበርም እሴቶቹን የሚያስጠብቅባቸው “ገደቦች”(constraints) ናቸው፡፡ ህጎች ከሃይማኖት እና ከእምነት ቀኖናዎች መንጭተው፣ የሰው ልጅ ራሱን ስርዓት ያሲያዘባቸው ሲሆኑ በኋላም አሻሽሎ እና አዘምኖ  ዘመናዊውን ህግ የቀረጸባቸው ናቸው፡፡ የሰው ልጅ ከንቁ አእምሮው(conscious mind) ይልቅ ኢ-ንቁ አእምሮው(unconscious mind) እጅጉን የሚገዛው እና የሚቆጣጠረው ፍጡር ነው፡፡ ስሜቱ፣ ፍላጎቱ እና ምኞቱ እጅጉን ገደብ አልባ ነው፡፡ ይህም መሰሎቹን እንዲጎዳ (ራሱንም ጭምር) ያደርገዋል፡፡ ይህንንም ለመከላከልና የሰው ልጅ ሰብአዊነቱን እንዲያስተውል ህግ/መተዳደሪያ ደንብን ፈጥሮአል፡፡ የ“ነጻነቱ”(mobility) እና “የገደቡ“(constraint) መጠን ይለያይ እንጂ በየትኛውም ማህበረሰብ ውስጥ ህግ አለ፡፡ ያለ ህግ/መተዳደሪ ደንብ የሚኖር ማህበር የለም፡፡
ሃይማኖትም ሆነ እጅጉን ለሰው ልጅ እንደ ግለሰብም ሆነ እንደማህበር አስፈላጊ የሆነው ህግ/መተዳደሪያ ደንብ በ“ኮተት” ይካዳል፡፡ ኮምቡጠር ሌሎች እሴቶች ላይ እና እሴቶቹ የተመሰረቱባቸው መርሆዎች ላይ የሚያደርገው ትችት፣ ሃይማኖት እና ህጎች/መተዳደሪያ ደንቦች ላይም በተመሳሳይ መልኩ በጉልህ ይታያል፡፡ ገፀባህሪው የሰው ልጅ ያለ ሰዋዊ እሴቶች መኖር ይችላል ብሎ ያምናል። ይህንንም ይሰብካል፡፡ አስተሳሰቡ ፍፁም ሊባል በሚችል ደረጃ ኒሂሊዝማዊ፣ ገፀባህሪውም ኒሂሊዝምን የሚያራምድ ኒሂሊስት ነው፡፡
“ኮተት” ኒሂሊዝምን ጭብጡ ያደረገ፣ ይህንንም በቅጡ ማሳካት የቻለ ድርሰት ነው፡፡ ለዚህም ደራሲው የተጠቀማቸው ሁለት ብልሀቶች ትልቁን ሚና ተጫውተዋል፡፡ አንደኛው ደራሲው የሳላቸውን ሁለት ተቀናቃኝ ገፀባህሪያት (አቶ አልአዛር እና ኮምቡጠር) ተመጣጣኝ አቅም እንዳይኖራቸው ማድረጉ ነው፡፡ እሴቶቹን የሚቃወመው የኮምቡጠር አቅምና የሀሳብ ትጥቅ እሱን ከሚቃወሙት ከአቶ አልአዛር አቅም የላቀና የደረጀ ነው፡፡ በአንጻሩ ሀሳቡን የሚቀናቀኑት  አቶ አልአዛር ይህንን አስተሳሰብ የሚቃረኑ ቢመስሉም የቱም ጋ የኮምቡጠርን አስተሳሰብ የሚገዳደር ሀሳብ ሲሰነዝሩ አይስተዋልም፡፡ የሀሳብ ትጥቃቸው እጅግ ደካማ በመሆኑም ከማመናጨቅና ከመሳደብ ውጪ ለትችቱ ተፈታታኝ ምላሽ አይሰጡም፡፡ ይልቁንም ኮምቡጠር ብዙ እንዲናገር የሚፈልጉ ናቸው፡፡ ደራሲው የኮምቡጠር ሀሳብ ሚዛን እንዲደፋና ተፅእኖ እንዲፈጥር ሲል የአቅም አለመመጣጠኑን ሆነ ብሎ በማድረግ በድርሰቱ ላይ የኒሂሊዝም ርዕዮት ጎልቶ እንዲወጣና እንዲያሸንፍ ያደረገ ይመስላል፡፡
ሁለተኛው ብልሀት ኒሂሊዝማዊ አስተሳሰብን የሚያራምደው ኮምቡጠር ውሻ ሆኖ መሳሉና እንዲሰክር መደረጉ ነው፡፡ ውሻ በመሆኑ የሰው ልጅ እሴቶች አይመለከቱትም፡፡ እሱ ውጪ ነው፡፡ ውጪ ያለ ደግሞ ይታዘባል፡፡ የታዘበ ደግሞ ትዝብቱን የሚናገርበት አጋጣሚ ይፈልጋል፡፡ ደራሲው ደግሞ አጋጣሚ ፈጥሮለታል፡፡ በአረቄ የራሰ ክትፎ አስኮምኩሞ “አስክሮታል”፡፡ የሰከረ ደግሞ የልቡን አይሸሽግም፤ ይናገራል፡፡ ይሉኝታ የለውም፤ አያመነታም፡፡ (“ሆድ ያባውን”… እንዲል የሀገሬ ሰው) ኮምቡጠርም ደራሲው የሰጠውን አቅምና አጋጣሚ በሚገባ ተጠቅሞ ኒሂሊዝምን ሰብኮአል፡፡ ሰውን “…ኮተታም ዘር!” እያለ፡፡
መልካም ሰንበት!!

Published in ጥበብ
Saturday, 16 August 2014 11:18

የፍቅር ጥግ

ባሎች እንደ እሳት ናቸው፤ ካልተከታተሏቸው ይጠፋሉ፡፡
Zsa Zsa Gabor
(ትውልደ ሃንጋሪ አሜሪካዊ የፊልም ተዋናይ)
ሚስቶች ለወጣት ወንዶች ውሽሞች፣ ለጎልማሶች ጓደኞች፣ ለአዛውንቶች ነርሶች ናቸው፡፡
ፍራንሲስ ቤከን
(እንግሊዛዊ ፈላስፋ፣ የፖለቲካ ሊቅና የህግ ባለሙያ)
ከ13 ዓመት ተኩል ዕድሜዬ ጀምሮ ከአስር ሺ ሴቶች ጋር ተኝቻለሁ፡፡
ጆርጅስ ሳይመን
(ትውልደ ቤልጂየም ፈረንሳዊ ፀሐፊ)
ሚስቱ ግን “ትክክለኛው ቁጥር ከ1200 አይበልጥም” ብላለች
በየምስቅልቅሉ አንድ ወዳጅ፣ በየወደቡ አንድ ሚስት አገኛለሁ፡፡
ቻርልስ ዲብዲን
(እንግሊዛዊ ተዋናይ፣ አቀናባሪና ጸሐፌ ተውኔት)
ሴቶች እንደ ባንክ ናቸው፤ ሰብሮ መግባት ትልቅ ሥራ ነው፡፡
ጆ ኦርቶን
(እንግሊዛዊ ፀሃፌ ተውኔት)
ፍቅር የሌለበት ትዳርና ትዳር የሌለበት ፍቅር አንድ ናቸው፡፡
ኬኔዝ ክላርክ
(እንግሊዛዊ የሥነ-ጥበብ ታሪክ ምሁር)
ገንዘብ ፍቅር ስለማይገዛልኝ፣ ለገንዘብ ብዙም ደንታ የለኝ፡፡
ጆን ሊኖን
(እንግሊዛዊ የሮክ ሙዚቃ አቀንቃኝ)

Published in የግጥም ጥግ
Page 8 of 20