ወጪው የኮሌጅ ክፍያን አያካትትም

በአሜሪካ ወላጆች አንድን ልጅ ከተወለደበት ጊዜ አንስቶ 18 አመት እስኪሞላው ድረስ በወጉ ተንከባክቦ ለማሳደግ የኮሌጅ ክፍያን ሳይጨምር ግማሽ ሚሊዮን  ዶላር ያህል ወጪ እንደሚጠይቃቸው ሲኤንኤን ዘገበ፡፡
አሜሪካውያን ወላጆች አንድን ልጅ ለማሳደግ ወጪ የሚያደርጉት ገንዘብ እንደገቢያቸው መጠን የሚለያይ መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፤ አነስተኛ ገቢ ያላቸው የአገሪቱ ወላጆች ከ145 ሺህ በላይ፣ መካከለኛ ገቢ ያላቸው ከ245 ሺህ በላይ፣ ከፍተኛ ገቢ ያላቸው ደግሞ 455 ሺህ ያህል ዶላር ወጪ እንደሚያደርጉ ገልጿል፡፡
ወጪዎቹ የተሰሉት ወላጆች ለቤት፣ ለምግብ፣ ለትራንስፖርት፣ ለአልባሳት፣ ለጤና፣ ለትምህርትና ለሌሎች ጥቃቅን ጉዳዮች የሚከፈሉ ገንዘቦችን መሰረት በማድረግ ሲሆን ባለፉት አመታት ለጤናና ለልጆች እንክብካቤ የሚወጣው ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መምጣቱን ዘገባው አስረድቷል፡፡
በአገሪቱ እየናረ የመጣው የትራንስፖርትና የምግብ ዋጋ ለአሜሪካውያን ወላጆች ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ እንደሚገኝ የጠቆመው ዘገባው፤ ባለፉት አስር አመታት የነዳጅ ዋጋ በእጥፍ መጨመሩንና የምግብ ዋጋም ባለፉት ስድስት አመታት ከ13 በመቶ በላይ ጭማሪ ማሳየቱን አመልክቷል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

ከ162 አገራት ‘ከግጭት ነጻ’ የሆኑት 11 ብቻ ናቸው ተባለ

ግጭት ባሉባቸው የዓለም አካባቢዎች ጦርነትን የማስቆምና ዓለምን ሁሉም ሰው ያለስቃይና ያለጦርነት ፍርሃት የሚኖርባት ሰላማዊ ስፍራ የማድረግ ዓላማ ያለው ዓለምአቀፍ የሰላም ጉባኤ በመጪው መስከረም መጀመሪያ በደቡብ ኮሪያ ሴኡል ከተማ እንደሚካሄድ አዘጋጆቹ ለአዲስ አድማስ አስታወቁ፡፡
የኡራጋይ፣ የኖርዌይና የኮስታ ሪካን ፕሬዚዳንቶች ጨምሮ የተለያዩ የአለም አገራት መሪዎችና የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች እንደሚሳተፉበት የሚጠበቀውን ይህን አለማቀፍ የሰላም ጉባኤ የሚያዘጋጀው፣ “ሄቨንሊ ካልቸር፣ ዎርልድ ፒስ፣ ሪስቶሬሽን ኦፍ ላይት” (HWPL) የተባለ የሰላም ባህልን በማህበረሰቦችና በዓለም አቀፍ ደረጃ በማጎልበት ጦርነትን ለማስቆም የሚሰራ መንግስታዊ ያልሆነ ዓለም አቀፍ ተቋም ነው፡፡
በመላው ዓለም በሃይማኖቶች መካከል ያሉ አለመግባባቶች ትላልቅ ግጭቶችን እንዳስከተሉ ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ የጠቆመው ተቋሙ፤ ሰላምን ለመፍጠር አስቀድሞ በሃይማኖቶች መካከል ሰላምና መግባባት ማስፈን የሚል ተልዕኮ እንዳለው አስታውቋል። ከመላው ዓለም ከ40 አገራት የተወከሉ ተሳታፊዎች በሚገኙበት የሴኡሉ ታሪካዊ የሰላም ጉባኤ ግጭቶችን በማስቆም ላይ ያተኮሩ ውይይቶች፣ ባህላዊ ትርኢቶችና የሰላም የእግር ጉዞ እንደሚደረጉ ይጠበቃል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ በፊሊፒንስ በሃይማኖት ልዩነቶች በግጭት በምትታመሰው ዛምቦዋንጋ ከተማ ተጨባጭ የሰላም መፍትሄ ለማምጣት ያለመ ዓለም አቀፍ የሰላም ጉዞ ማካሄዱን ተቋሙ አክሎ ገልጿል። ባለፈው ነሐሴ 5 ለ3 ቀናት ተጀምሮ በተካሄደው 13ኛው የሰላም ጉዞ በዛምቦአኛ ከተማ በሚንዳናኦ ደሴት የፊሊፕንስ መንግስት ከፍተኛ አመራሮችና የሃይማኖት መሪዎችን ጨምሮ 12ሺ የሚገመት ህዝብ የተሳተፈበት የሰላም የእግር ጉዞ የተካሄደ ሲሆን 300 የፊሊፒንስ ፖሊሶች የተካፈሉበት የሰላም ፎረም መካሄዱን ተቋሙ በመግለጫው ጠቁሟል። የተቋሙ ፕሬዚዳንት ሚ/ር ሊ፤ 3ሺ ለሚደርሱ ተማሪዎች ሰላም ላይ ያተኮረ ትምህርት እንደሰጡም ለማወቅ ተችሏል፡፡ የሰላም ልኡኩ ከዚህ ቀደምም ወደ ፊሊፒንስ ተጉዞ እንደነበር ያስታወሰው ተቋሙ፤ የካቶሊክና የሙስሊም ሃይማኖት ተወካዮችን አገናኝቶ የወንድማማችነት ስምምነት በማፈራረም በሚንዳናኦ ከ40 ዓመት በላይ የዘለቀውን የሁለቱን ሃይማኖቶች ግጭት እንዳስቆመ ጠቁሟል፡፡ የሰላም  ተቋሙ በመላው ዓለም ከሚገኙ 81 አገራትና ከ321 ከወጣቶች ጋር ትስስር ካላቸው ድርጅቶች ጋር በትብብር እንደሚሰራ ታውቋል፡፡
በሌላ በኩል፣ ‘ኢንስቲቲዩት ፎር ኢኮኖሚክስ ኤንድ ፒስ” የተባለ ዓለማቀፍ ተቋም በሰራው ጥናት፣ ባለፈው የፈረንጆች አመት በአለም ዙሪያ ከሚገኙ 162 አገራት ‘ከግጭት ነጻ’ የሆኑት 11 ብቻ እንደነበሩ በጥናት ማረጋገጡን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡በዘንድሮው የፈረንጆች አመት ከተለያዩ የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ግጭቶች የጸዱ ተብለው በጥናቱ የተለዩት አገራት ስዊዘርላንድ፣ ጃፓን፣ ኳታር፣ ሞሪሺየስ፣ ኡራጓይ፣ ቺሊ፣ ቦትስዋና፣ ኮስታ ሪካ፣ ቬትናም፣ ፓናማ እና ብራዚል ናቸው፡፡
እ.ኤ.አ ከ2007 ጀምሮ ባሉት አመታት የዓለማችን ሰላም ከጊዜ ወደጊዜ እየከፋ መምጣቱን የጠቆመው ዘገባው፣ ጥናቱ ከተሰራባቸው 162 አገራት ግጭት የሌለባቸው 11 ብቻ ሆነው መገኘታቸውም ለዚህ አለማቀፍ ችግር ማሳያ ነው ብሏል፡፡
ምንም እንኳን አስራ አንዱ አገራት በ2013 ከግጭት ነጻ እንደሆኑ በጥናቱ ቢረጋገጥም፣ አገራቱ ለግጭት ሊዳርጓቸው ከሚችሉ ሌሎች ችግሮች ነጻ አይደሉም ያለው ዘገባው፣ ለአብነትም በብራዚልና በኮስታ ሪካ የአገር ውስጥ ግጭቶች ችግር እጅግ በጣም አነስተኛ ቢሆንም፣ የአገራቱ ዜጎች አነስተኛ የጦር መሳሪያዎችን የማግኘት እድላቸው ከፍተኛ በመሆኑ ሃይል የተቀላቀለባቸው ተቃውሞዎች የመካሄዳቸው እድል በአሳሳቢ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን አስረድቷል፡፡
ጥናቱ በተሰራበት ወቅት ሰላማዊ የነበረችው ብራዚል ከወራት በፊት ባስተናገደችው የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ሳቢያ በተቀሰቀሰባት የህዝብ አመጽ የተነሳ በቀጣዩ አመት ይወጣል ተብሎ በሚጠበቀው የ2014 ከግጭት ነጻ አገራት ዝርዝር ውስጥ እንደማትኖር ዘገባው ገልጿል፡፡
አንድ አገር ከግጭት ነጻ ለመባል፣ ተቋሙ ያወጣቸውን የግጭት መለኪያ መስፈርቶችን በሙሉ ማሟላት እንደሚገባውና በአገሩ የግዛት ክልል ውስጥ በሁለት የታጠቁ ሃይሎች መካከል (ቢያንስ አንዱ መንግስት መሆን አለበት) በተፈጠረ ግጭት በአመት ውስጥ ከ25 በላይ የሞት አደጋ ያልተከሰተበት መሆን አለበት፡፡ በድንበር አካባቢም ግጭት መኖር የለበትም፡፡
አሜሪካ ተቋሙ ባወጣው የሰላማዊነት ደረጃ 101ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ዘገባው ጨምሮ ገልጿል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

ኢራናዊቷ የሂሳብ ባለሙያ ፕሮፌሰር ሜርያም ሚርዛካኒ፤ አለማቀፉ የሂሳብ ህብረት የሚሰጠውንና ከኖቤል ሽልማት ጋር የሚስተካከለውን የፊልድስ ሜዳል ሽልማት መቀበሏን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
በየአራት አመቱ በአለማቀፍ ደረጃ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የሂሳብ ተመራማሪዎች የሚሰጠውን ይህን ሽልማት በመውሰድ የመጀመሪያዋ የሆነችው ፕሮፌሰር ሚርዛካኒ፤ ትኩረቷን በጂኦሜትሪ ላይ በማድረግ፣ ሬማን ሰርፌስስ ከተባሉ ቅርጾች ጋር የተያያዘና ውስብስብ ሂሳባዊ ቀመር የሚጠይቅ የምርምር ውጤት ይፋ በማድረጓ ለሽልማት እንደበቃች ዘገባው ገልጿል፡፡
የአንደኛና የሁለተኛ እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርቷን በቴህራን የተከታተለችው ሚርዛካኒ፤ ወደ አሜሪካ በማቅናት የፒኤችዲ ትምህርቷን በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የተከታተለች ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም ካሊፎርኒያ በሚገኘው ስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነትና በተመራማሪነት እየሰራች ትገኛለች፡፡ 

Published in ከአለም ዙሪያ

አመታዊ የማስታወቂያ ገቢው 50 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል
ለስኬቱ የአንበሳውን ድርሻ የምትወስደው አንዲት ሴት ናት ተብሏል
ከአስርት አመታት በፊት በይዘትም ሆነ በአቀራረብ ጥራቱን ያልጠበቀና ደረቅ ፕሮፓጋንዳ የነበረው የቻይና የማስታወቂያ ዘርፍ፣ በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ በአመት 50 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ወደሚያስገኝ ዘመናዊ የማስታወቂያ ኢንዱስትሪነት መሸጋገሩንና፣ በዘንድሮው የዓለም የማስታወቂያ ገበያ ሁለተኛውን ደረጃ መያዙን ሲኤንኤን ዘገበ፡፡
የቻይና የማስታወቂያ ኢንዱስትሪ በአሁኑ ወቅት ከአውሮፓና ከሌሎች የአለም አገራት ታላላቅ የማስታወቂያ ኩባንያዎች ጋር ተፎካካሪ እንደሆነና በአትራፊነት የሚጠቀስ መሆኑን የጠቆመው ሲኤንኤን፣ ኢንዱስትሪው ከነበሩበት ችግሮች ተላቆ ዘመናዊ አደረጃጀትና አሰራር እንዲይዝ በማድረግ በኩል የአንበሳውን ድርሻ የምትወስደው ቻይናዊቷ የማስታወቂያ ባለሙያና ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሺናን ቹዋንግ እንደሆነች ገልጿል፡፡
በማስታወቂያው ዘርፍ ከ30 አመታት በላይ እንደቆየች የተነገረላት ቹዋንግ፤ በአሁኑ ወቅት በዘርፉ በአለማቀፍ ደረጃ ስማቸው ጎልቶ ከሚጠቀሱ የማስታወቂያ ድርጅቶች አንዱ የሆነውንና ትርፋማውን “ኦጊልቪ ኤንድ ማተር ግሬተር ቻይና” የተባለ የአገሪቱ ኩባንያ በዋና ስራ አስፈጻሚነት ከመምራት ባሻገር የቻይናን የማስታወቂያ ኢንዱስትሪ በአመት ከ50 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ የሚያገኝበት ደረጃ ላይ ያደረሰች ብርቱ ሴት መሆኗን ዘገባው ይጠቁማል፡፡
ቹዋንግ በማስታወቂያው ዘርፍ በቆየችባቸው አመታት በአገር አቀፍ ደረጃ ተቋማዊና የአሰራር ለውጥ በመፍጠር ረገድ ሰፋፊ ስራዎችን አከናውናለች ያለው ዘገባው፤ አሁን ዋና በስራ አስፈጻሚነት በምትመራው ኩባንያ፤ አለማቀፍ የጥራት ደረጃዎችን የጠበቁ ማስታወቂያዎችን በመስራት ትልቅ ስኬት መጎናጸፍ መቻሏን አመልክቷል፡፡
ኩባንያው በቴክኖሎጂ የታገዙና ፈጠራ የታከለባቸውን አለማቀፍ የምርትና የአገልግሎት እንዲሁም የቅስቀሳ ማስታወቂያዎች በብዛት በመስራት ላይ እንደሚገኝ ጠቁሞ፣ ኩባንያው ለኮካ ኮላ በሰራው ማስታወቂያ የ “ኬንስ ግራንድ ፕሪክስ”ን ሽልማት ለመቀበል መብቃቱንም አስታውሷል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

          አዲስ አበባ ለወደፊት በኢንቨስትመንት ዘርፍ ተመራጭ የሆኑ የአፍሪካ 10 ቀዳሚ አገራት በሚል ግሎባል ኢኮኖሚ ዎች በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት ውስጥ መካተቷን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ተቋሙ በአህጉሪቱ በቀጣይ ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻዎች ይሆናሉ ባላቸው ከተሞች ዝርዝር ውስጥ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ ኢባዳንና ካኖ የተባሉትን የናይጀሪያ ከተሞች፣ የቡርኪናፋሶዋን ኡጋዱጉ፣ የሴኔጋሏን ዳካር፣ የኬንያዋን ናይሮቢ፣ የኮትዲቯሯን አቢጃኒን፣ የሱዳኗን ካርቱም፣ የአንጎላዋን ሉዋንዳና የታንዛንያዋን ዳሬ ሰላም ማካተቱን ሚኒስቴሩ በድረገጹ ያወጣው መረጃ ያሳያል፡፡
ተጨባጭ የኢንቨስትመንት አማራጭ ያለባቸው ከተሞች በቀጣዮቹ ሁለት አስርት አመታት  በእጥፍ ያህል እንደሚያድጉ የተነበየው የተቋሙ ሪፖርት፣ እነዚህ ከተሞች ወደሌሎች አገራት የመስፋፋት ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙ የንግድ ተቋማት ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንደሚሆኑም አመልክቷል፡፡
በእነዚህ ከተሞች የሚካሄደውን የመሰረተ ልማት አውታሮች የማስፋፋት እንቅስቃሴ በተፋጠነ ሁኔታ አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ያለው ሪፖርቱ፣ የመሰረተ ልማት አውታሮች መስፋፋት በአህጉሪቱ እድገትን ለማፋጠን ቁልፍ ሚና እንደሚጫወትና ማህበረሰቡን ያቀፈ ዘላቂ እድገት ለማስመዝገብ ወሳኝ እንደሆነ ጨምሮ ገልጧል፡፡ 

አለማቀፍ የቡና ገበያንና ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው

ኢትዮጵያ በመጪዎቹ አስራ ሁለት ወራት ለውጭ ገበያ ከምታቀርበው የቡና ምርት የምታገኘው ገቢ በ25 በመቶ እድገት ያሳያል ተብሎ እንደሚጠበቅ ብሉምበርግ ዘገበ፡፡
በቡና ምርትና በአቅራቢነት ከአለም ቀዳሚ በሆነችው ብራዚል በተከሰተው ድርቅ ምክንያት በአለም የቡና ገበያ ላይ የዋጋ ጭማሪ ይፈጠራል ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለጸው ዘገባው፣ ኢትዮጵያም በተያዘው የፈረንጆች አመት ለውጭ ገበያ ከምታቀርበው የቡና ምርት 900 ሚሊዮን  ዶላር ያህል ገቢ ታገኛለች ተብሎ እንደሚጠበቅ ዘገባው አመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አለምሰገድ አሰፋን ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ የአለም ገበያ የቡና አቅርቦት እጥረት የሚቀጥል ከሆነ በኢትዮጵያ የምርት ገበያ አማካይነት ለገበያ በሚቀርበው የአረቢካ ቡና ዋጋ ላይ በፓውንድ የ2 ዶላር ጭማሪ ሊገኝ ይችላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ኢትዮጵያ እስካለፈው ሃምሌ ወር መጀመሪያ በነበሩት 12 ወራት ለውጭ ገበያ ካቀረበችው ቡና 719 ሚሊዮን ዶላር ማግኘቷን ያስታወሰው ዘገባው፣ ይህም ከአንድ አመት በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር የ3 ነጥብ 7 በመቶ ብልጫ እንዳለው ጠቅሷል። በተመሳሳይ ጊዜ ለውጭ ገበያ ባቀረበችው የቡና ምርት መጠን ላይ የ4 ነጥብ 1 በመቶ ቅናሽ መታየቱንም አመልክቷል፡፡
በዚህ አመት በአገሪቱ 500 ሺህ ቶን ቡና ይመረታል ተብሎ እንደሚጠበቅና፣ ከዚህ ውስጥም ግማሽ ያህሉ ወደተለያዩ አገራት ገበያ የሚላክ እንደሚሆንም ዘገባው ጨምሮ ገልጧል፡፡
የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ከተለያዩ የአለም አገራት አዳዲስ የቡና ምርት ገዢዎችን ለመሳብና አገሪቱ በአለማቀፉ የቡና ገበያ ውስጥ ያላትን ድርሻ ለማሳደግ እየሰራ እንደሚገኝም አስታውቋል፡፡ ወርልድ ቡሊቲን በበኩሉ፤ ከአፍሪካ ቀዳሚዋ የቡና አምራች የሆነችው ኢትዮጵያ ለአለም ገበያ የምታቀርበውን የቡና ምርት የንግድ ምልክት በማውጣት የበለጠ በገበያው ውስጥ ተወዳዳሪ ለማድረግ በአለማቀፍ ደረጃ ታዋቂ ከሆኑ ቡና ገዢ ኩባንያዎች ጋር እየሰራች መሆኗን ዘግቧል፡፡
ከኩባንያዎቹ ጋር የተጀመረው ስራ ህገወጥ የቡና ንግድንና አላግባብ የሚጣል የቡና ዋጋ ተመንን የመከላከል እንዲሁም የአገሪቱን የቡና የንግድ ምልክቶች በመጠቀም ትርፋማነትን የማሳደግ ዓላማ ያለው ነው ተብሏል፡፡
በአገሪቱ በቡና ልማት ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳትፎ የሚያደርጉ 15 ሚሊዮን ዜጎች እንዳሉ የጠቆመው ዘገባው፣ እነዚህ ዜጎች ከሽያጩ የሚያገኙት ገቢ ከ10 በመቶ በታች እንደሆነና የተቀረውን የሚወስዱት በአለማቀፍ ደረጃ የሚገኙ ነጋዴዎችና አከፋፋዮች መሆናቸውን ገልጧል፡፡
እስካሁን ድረስ 34 አገራት በደቡብና በምስራቅ ኢትዮጵያ የሚመረቱ የቡና ዝርያዎች መለያዎችንና የንግድ ምልክቶችን ተቀብለው ለገበያ እያቀረቡ እንደሚገኙ ገልጾ፣ በቀጣይም በአውስትራሊያና በብራዚል ተመሳሳይ ስራ ለመስራት እንቅስቃሴ መጀመሩን አስረድቷል፡፡

       የብሄራዊ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የስማርት ቴክኖሎጂ ውጤት የሆኑ የኤሌክትሪክ ቆጣሪዎችን አምርቶ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ማቅረብ የጀመረ ሲሆን ቴክኖሎጂው በሃገር ውስጥ መሰራቱ የሃገር ደህንነትን ለማስጠበቅ ከፍተኛ ፋይዳ አለው ተብሏል፡፡
ከውጭ በከፍተኛ ምንዛሬ የሚገቡትን ቆጣሪዎች ሙሉ ለሙሉ እንደሚያስቀር የተነገረለት የኤሌክትሪክ ቆጣሪ “አይቲ ፕላስ ስማርት ኢነርጂ ሜትር” በመባል የሚታወቅ ሲሆን እስካሁን ከሚሰራበት ቴክኖሎጂ በተሻለ ሁኔታ መስራት የሚችሉ የተለያዩ አገልግሎቶችን ያካተተት ነው ተብሏል፡፡
የብኢኮ ም/ዋና ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄነራል ጠና ቁርንዲ ከትናንት በስቲያ ከስራ ባልደረቦቻቸው ጋር በሒልተን ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳስታወቁት፤ ቆጣሪው የወደፊቱን የቴክኖሎጂ እድገት እያንዳንዱ ቆጣሪ ያለሰው ንክኪ ከዋና ማዕከል ጣቢያ ጋር በርቀት መቆጣጠሪያ እየተገናኘ የሚሰራበት በመሆኑ በኃይል አቅርቦት ላይ ያነጣጠሩ ሃገራዊ የደህንነት ስጋቶችን መቆጣጠርና መከላከል ያስችላል ብለዋል።
ደህንነትን ያስጠብቃል የተባለው የኤሌክትሪክ ቆጣሪው፤ ከንድፉ እስከ ምርት ድረስ በብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን እና በስሩ ባሉት ተቋማት የተፈበረከ ሲሆን የፕላስቲክ ክፍሉ በኢትዮ ፕላስቲክ ኢንዱስትሪ፣ የብረታ ብረት ክፍሉ ደግሞ በብረታ ብረትና ፋብሪኬሽን ኢንዱስትሪ እንዲሁም የተለያዩ ምርቶች በህብረት ማኑፋክቸሪንግ ማሽን ግንባታ ኢንዱስትሪ የተመረተ ነው ተብሏል፡፡ ፋብሪካው ሙሉ ለሙሉ ወደ ስራ ሲገባም በቀን 1200 ቆጣሪዎችን የማምረት አቅም አለው ተብሏል፡፡
የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ ሲስተም ለጦርነት ጥቃት እንደሚውል ይታወቃል ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ ብ/ጄነራል ጠና ቴክኖሎጂው ሙሉ ለሙሉ የሃገር ውስጥ መሆኑ በኃይል ላይ አነጣጥሮ የሚፈፀም የጦር ጥቃትን በቀላሉ ለመቆጣጠር እንደሚያስችል ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋየር ቢዝነስ ስራ አስፈፃሚ አቶ ቢትወደድ ገ/አሊፍ በበኩላቸው፤ “ቴክኖሎጂው በደንበኛውና በአገልግሎት አቅራቢው መካከል ጥብቅ ቁርኝትን ይፈጥራል፤ ቆጣሪ አንባቢነትን አስቀርቶም ደንበኞች የራሳቸውን ሂሳብ አውቀው በቢል መልክ እንዲከፈሉ ያስችላል” ብለዋል፡፡ ቆጣሪ አንባቢነት ቢቀርም የሚፈናቀል ሰራተኛ አይኖርም፤ ሌሎች ስራዎች ይሰጣቸዋል ሲሉ ኃላፊው ጨምረው ገልፀዋል፡፡
አዲሱ ስማርት ቆጣሪ በርቀት መቆጣጠሪያ የሚታገዝ በመሆኑም አደጋ ሲያጋጥም በቀላሉ ለዋና ማዕከል መልዕክት ስለሚያስተላልፍ ኃይል በመቀነስ መቆጣጠር ያስችላል፤ ቆጣሪው ንክኪ ሲደረግበት በቀጥታ ለማዕከሉ መረጃ ያቀብላል ተብሏል፡፡
ኢብኮ አንዱን ቆጣሪ በ2500 ብር ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚያቀርብ መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን ቆጣሪው በቅርቡ አገልግሎት ላይ እንደሚውል ተገልጿል፡፡


             መንግስት እንደሚለው፤ ጋዜጠኞችን የሚያዋክበውና የሚያስረው በርካታ ጋዜጠኞች ስርዓት አልበኛና ነውጠኛ ስለሆኑ ይሆን? ወይስ አንዳንድ ተቃዋሚዎች እንደሚሉት፤ መንግስት በጭራሽ የነፃነትን ጭላንጭል የማይፈቅድ የለየለት አምባገነን ስለሆነ?
እንደምታውቁት፤ በዚህ አሳዛኝና አሳሳቢ የአገሪቱ እውነታ ውስጥ፤ “ሕዝቡ” የለበትም። በዚህ ላይ መንግስትና ገዢው ፓርቲ፣ እንዲሁም አብዛኞቹ ተቃዋሚዎችና ፖለቲከኞች ይስማሙበታል። በቃ! “ሕዝቡ”... ለእውነት የቆመ፣ ነፃነት ወዳድ፣ በቅንነነትና በፍትህ የሚያምን፣ ኩሩና የሰላማዊ ነው። ችግሩ ያለው ሌላ ጋ ነው። ማን ጋ? እዚህኛው ጥያቄ ላይ፣ ልዩነት ይመጣል። መንግስት፣ “አመኛ” የሚላቸውን ተቃዋሚ ፓርቲዎችና “የተቃዋሚዎች ልሳን” የሚላቸውን ጋዜጠኞች ይወነጅላል። ተቃዋሚዎች በበኩላቸው፣ መንግስትንና ገዢውን ፓርቲ ይኮንናሉ። እስቲ ሁለቱንም በየተራ እንመልከታቸው።
በቅርቡ በነፃ መፅሔቶች ላይ በቀረበው ክስ ውስጥ ተደጋግሞ የተጠቀሰ ነገር አለ - መፅሔቶቹ አመፅን ይቀሰቅሳሉ የሚል። ገና በፍርድ ቤት ባይረጋገጥም፣ እንዲያው ነገሩ እውነት ቢሆን እንኳ፤ እንደ ወንጀል ተቆጥሮ ያስከስሳል ወይ? አመፅን የሚቀሰቅስ ሁሉ አይከሰስም -  ጉዳት ካደረሰ ወይም ደግሞ ካሁን አሁን ጉዳት ያደርሳል የሚል አጣዳፊ ስጋት ካልተከሰተ በቀር። የአመፅ ቅስቀሳ በተጨባጭ አመፅን ካልፈጠረ በቀር ሊያስከስስ አይገባም ማለቴ አይደለም። የአመፅ ቅስቀሳው ለጊዜው ጉዳት ባያደርስም፣ ቢያንስ ቢያንስ አስጊ ከሆነ ... ያኔ ክስ ሊመጣ ይችላል - በግልፅ የሚታይ ደራሽ አደጋ የሚጥር ከሆነ ማለት ነው - (clear and present danger) እንደሚባለው።
ሁለት ምሳሌዎችን ልጥቀስላችሁ። የሶሻሊዝምና የኮሙኒዝም ሃሳቦችን ማሰራጨት፣ ያለ ጥርጥር አመፅን ከመቀስቀስ የተለየ ትርጉም የለውም። የግል ንብረትን ለመውረስና የአንድ “አብዮታዊ ፓርቲ” አምባገነንነትን ለማስፈን፣ ከአመፅ ውጭ ሌላ አማራጭ የለም በማለት የሚሰብኩ ናቸውና። ነገር ግን፤ አያስከስሱም። ለምን? ዛሬ ቅስቀሳው አመፅን አልፈጠረም፤ አጣዳፊ አደጋ ይፈጥራሉ ለማለት የሚስችል ምልክት የለም።
ሌላ መረጃ ልጨምርላችሁ። የአገሪቱ መንግስት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ነባሮቹ የሃይማኖት ተቋማት፣ የንግድ ስርዓቱ ሁሉ የሰይጣን ተወካዮች ናቸው ብለው የሚያምኑ ሰዎች፤ በይፋ እምነታቸውን ይሰብካሉ፤ መንግስትን ጨምሮ የሰይጣን ተወካዮች የተባሉት ተቋማት በሙሉ እንደሚፈራርሱና አመድ እንደሚሆኑ ዘወትር ይሰብካሉ፤ ያንንም ጊዜ ይናፍቃሉ። ግን፣ አመፅ አልፈጠሩም፤ አልያም የአመፅ ጥፋት ለመፍጠር አፋፍ ደርሰዋል የሚያስብል የአደጋ ፍንጭ የለም። ስለዚህ ምንም የሚያስከስስ ወንጀል አልሰሩም። እንዲያውም፤ መንግስታዊው ስርዓት የሰይጣን ተወካይ ነው ብለው መስበክ መብታቸው ስለሆነ ነው፤ በይፋ መፅሔት የሚያሰራጩት፤ በየመንገዱ የሚሰብኩት፤ በየሳምንቱ ከደርዘን በላይ በሆኑ አዳራሾች ጉባኤ የሚያካሂዱት።
 በአመፅ “አብዮታዊ አምባገነንነትን” ለማስፈን የሚቀሰቅሱ ቅሪት የኮሙኒዝም አፍቃሪዎችም ሆኑ፣ “መንግስት የሰይጣን እንደራሴ ነው” ብለው የሚያምኑ ሰባኪዎች፡ “ያንን ፃፋችሁ፤ ይሄንን ተናገራችሁ፤ መፅሔት አሳተማችሁ፣ በራሪ ወረቀት በተናችሁ” ተብለው አይከሰሱም። ለምን? አሁን የፈጠሩት አመፅ የለም፤ አሁን የጥፋት አፋፍ ላይ የደረሰ አጣዳፊ አደጋም የለም። ስለዚህ ወንጀል አልፈፀሙም። ወንጀል ካልፈፀሙ ደግሞ፣ መታሰርና መዋከብ የለባቸውም።
“ወንጀል አልሰሩም፣ ሃሳባቸውን ቢገልፅና ቢሰብኩ መብታቸው ነው” ሲባል ግን፤ “ሃሳባቸው ትክክልና ጠቃሚ ነው” ማለት አይደለም። ሃሳባቸው፣ ሙሉ ለሙሉ ስህተት ነው፤ ጎጂ ነው። ነገር ግን፤ “ሃሳባቸው የተሳሳተ ነው፤ ወደፊት ጉዳት ያደርሳል” የምንል ከሆነ፣ ከእነሱ ተሽለን ትክክለኛና ጠቃሚ ሃሳብ እስከያዝን ድረስ መፍትሄው ቀላል ነው። ተአማኒነት እንዳይኖራቸውና “ሆ” ብሎ የሚጎርፍ ተከታይ እንዳያገኙ፣ በሃሳብ ተከራክረን ልናሸንፋቸው እንችላለን - ስህተታቸውንና ጉድለታቸውን በግልፅ በማሳየትና ትክክለኛውንና ጠቃሚውን ሃሳብ በማቅረብ። “መተማመኛህ ምንድነው?” በሉ።
ገዢው ፓርቲና ተቃዋሚዎች እንደሚሉት፣ “ህዝቡ” ቅዱስ ከሆነ፣ ... አብዛኛው ሰው ለእውነት በመቆምና ነፃነት በመውደድ የእኔነት ክብር የተጎናፀፈ ከሆነ፤ ... ማለትም አገሪቱ የስልጡን አስተሳሰብ ባለቤት ከሆነች... ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ይሆናል።
የአመፅ ቅስቀሳ ከየትም ቢመጣ ሰሚ አያገኝም፤ እያሰለሰ የሚያስርና የሚያዋክብ አምባገነንም አይኖርም። “በስልጡኑና በአስተዋዩ ሕዝባችን” ፊት እየቀረቡ በመከራከር ብቻ ማሸነፍ ይቻላል። መቼም “ሕዝቡ” ስልጡን እስከሆነ ድረስ፣ በሃሳብ ክርክር ላይ፤ ከተሳሳተና ከጎጂ ሃሳብ ይልቅ፣ ትክክለኛና ጠቃሚ ሃሳብ ብልጫ ይኖረዋል። በሌላ አነጋገር፤ ትክክለኛ አስተሳሰብ ካልያዝን ነው፤ ወደ እስርና ወደ ወከባ የምንቸኩለው።
አሁን፣ “አመፅን ቀስቅሰዋል” ተብለው ወደ ተከሰሱት መፅሄቶች እንመለስ። የመጀመሪያው ጥያቄ፣ “አመፅ ቀስቅሰዋል የተባሉት መፅሔቶች፣ በእርግጥ አመፅ ፈጥረዋል ወይ?” የሚል ነው። እስካሁን፣ መፅሄቶቹ አመፅ ስለመቀስቀሳቸው እንጂ አመፅ ስለመፍጠራቸው በመንግስት የተነገረ መረጃ የለም። ይሄ አያከራክረንም። ወደ ሁለተኛው ጥያቄ እንሻገር - “አፋፍ ላይ የደረሰ ግልፅ የአደጋ ስጋትስ ተከስቷል ወይ?”
ስጋትማ መች ይጠፋል ብትሉ አይገርመኝም። ደግነቱ፣ ከሌላው ጊዜ ጋር ሲነፃፀር፣ ዛሬ በአመዛኙ የተረጋጋ ሁኔታ ይታያል። “ሁሉም ነገር አማን ነው” ማለት ግን አይደለም። ኢትዮጵያ እንደ ብዙዎቹ ኋላቀር አገራት በቀላሉ ለአደጋ የምትጋለጥና ብዙም ከስጋት ያልራቀች አገር ናት። እንዲያም ሆኖ መንግስት፣ “በመፅሔቶቹ ምክንያት ስጋት ላይ ወድቄያለሁ” ብሎ በጭራሽ የሚናገር አይመስለኝም።
ደግሞስ፣ በሳምንት አንዴ የሚሰራጩ በጣት የሚቆጠሩ መፅሔቶች እንዴት ለመንግስትና ለገዢው ፓርቲ ትልቅ ስጋት ሊሆኑ ይችላሉ? በየእለቱ ከጥዋት እስከ ማታ የሚሰራጩ በደርዘን የሚቆጠሩ የቲቪና የሬድዮ ጣቢያዎችን ይዞ፤ በመቶ የሚቆጠሩ ጋዜጠኞችንና በሺ የሚቆጠሩ የ”ኮሙኒኬሽን” ባለሙያዎችን ያሰማራ መንግስት፤ ከመሃል አገር እስከ ጠረፍ ድረስ እልፍ ካድሬዎችን አሰማርቶ፣ ከደርዘን በላይ ግዙፍ ማህበራትንና በሚሊዮን የሚቆጠሩ አባላትን ያደራጀ ገዢ ፓርቲ፣ እንዴት በጣት የሚቆጠሩ መፅሔቶችን በክርክር ማሸነፍ ይሳነዋል? በ“ሕዝቡ” ዘንድ ተአማኒነት እንዳይኖራቸውና ለአመፅ “ሆ” ብሎ የሚነሳ ተከታይ እንዳይኖራቸው ማድረግ አቅቶት ስጋት ላይ ይወድቃል?
መንግስትም ሆነ ገዢው ፓርቲ፣ ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሚኖራቸው አይመስለኝም። ለዚህም ነው፤ መንግስት “በመፅሔቶቹ ምክንያት አገሪቱ ስጋት ላይ ወድቃለች” ብሎ ሊናገር የማይችለው። አሃ! በአራት መፅሔቶች ሳቢያ የአገሪቱ የመንግስት ስጋት ላይ ከወደቀ፤ ... ወይ መንግስት ትክክለኛና ጠቃሚ ሃሳብ አልያዘም፤ አልያም “ሕዝቡ” ለትክክለኛና ለጠቃሚ ሃሳብ ጆሮ የለውም ማለት ነው።    
ያው፣ እንደተለመደው መንግስትና ገዢው ፓርቲ፤ “ፈፅሞ እንከን የለብንም፣ ትክክለኛና ጠቃሚ ሃሳብ ይዘናል” ባይ ናቸው። ስለዚህ ችግሩ ያለው፣ “ሕዝቡ” ላይ ሳይሆን አይቀርም። አመፅ ይቀሰቅሳሉ በሚል የተከሰሱት መፅሔቶች ለመንግስት ስጋት ሊሆኑ የሚችሉት፣ ነውጥ የሚያፈቅርና በትንሽ ቅስቀሳ “ሆ” ብሎ ለመትመም የተዘጋጀ አስተዋይነት የጎደለው ኋላቀርና ግልብ “ህዝብ” ካለ ብቻ ነው።
“ሕዝቡ”፤ ለትክክለኛና ለጠቃሚ ሃሳብ ጆሮ የሌለው፣ በቀላሉ የሚታለል፣ እንደ ከብት እየተነዳና እየተንጋጋ ነውጥን የሚደግፍ ወራዳ ካልሆነ፣ ችግር አይፈጠርም። ለእውነትና ለነፃነት በመቆም የእኔነትን ክብር የተጎናፀፈ “ሕዝብ” ውስጥ፤ የነውጥ ቅስቀሳ ጉዳት አያደርስማ። “የምፅአት ቀን ደርሷልና ወደ ፅዮን ተራራ ውጡ” ብሎ በእንግሊዝና በአሜሪካ ጎዳናዎች ላይ ከሚቀሰቅስ ሰባኪ የተለየ አይሆንም - በዛሬ ዘመን ብዙ ሰሚ አያገኝም፤ ቢሰሙትም ተከታይ ሆነው አይጎርፉለትም።
ልክ እንደዚያው፣ መንግስት እንከን አልባ ከሆነና “ሕዝቡ” ስልጡን ከሆነ፤ በጣት የሚቆጠሩ መፅሔቶች በሳምንታዊ ሕትመት ብቻ ሳይሆን ነጋ ጠባ አመፅ ቢቀሰቅሱ እንኳ ቅንጣት ታህል ስጋት መፍጠር አይችሉም። በእንከን አልባው መንግስት ላይ ስጋት መፍጠር ከቻሉ ግን፤ ያለ ጥርጥር “ሕዝቡ” ላይ ችግር አለ። “ሕዝቡ” ክፉ የአመፅ ጥም አለበት፤ አልያም በጥቂት ቅስቀሳ የሚንጋጋ ተላላ ሞኝ ነው። የዚህን ያህል እጅግ የባሰበት ኋላቀርነት ውስጥ ባይዘፈቅ እንኳ፣ ቢያንስ ቢያንስ የኋላቀርነት ዝንባሌ የተጠናወተው መሆን አለበት። እንዴት? ያው፣ ቅስቀሳ እስካልሰማ ድረስ፣ ጨዋ ይሆናል። ቅስቀሳ የሰማ ጊዜ ግን፤ ናላው ይዞራል፤ ለነውጥ ይነሳል - በሌላ አነጋገር ለነውጥና ለተላላነት የተጋለጠ ነው። “አይ፤ ሕዝቡን አትንካ” ከተባለ፤ ሌላኛ አማራጫችን ጣታችንን መንግስት ላይ መቀሰር ይሆናል። ብዙዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በዚህ ይስማማሉ።
እና ተቃዋሚዎች እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን በማሰርና በማዋከብ የአለም መሪ ለመሆን የምትፎካከረው፣ መንግስት የለየለት አምባገነን ስለሆነ ይሆን? በእርግጥ፣ መንግስት የለየለት አምባገነን ከሆነ፣ ዛሬ ጋዜጠኞችን አሰረ ወይም አዋከበ ብለን እንደ አዲስ የምንገረምበት ምክንያት አናገኝም። እንዲያውም፤ ሳይታሰሩ የቆዩ ጋዜጠኞችና ሳይዘጉ የቆሙ መፅሔቶች መኖራቸው ነው የሚገርመን።
በሌላ አነጋገር፤ ገዢው ፓርቲ የለየለት አምባገነን ከሆነ፣ የግል ነፃ ጋዜጣና መፅሔት የሚባል ነገር ሊኖር አይችልም፤ እንደ ኤርትራ ወይም እንደ ሰሜን ኮሪያ። ጥሩ! ገዢው ፓርቲ “የለየት አምባገነን” ባይሆንም እንኳ... ተራ አምባገነን ቢሆንኮ በቂ ነው። ማሰርና ማዋከብ የዘወትር ስራው ያልሆነ፣ ሰበብ ካገኘ ግን የማያልፍ. ወይም እያሰለሰ የሚነሳበት ለተራ አምባገነን ጋዜጠኞችን የሚያስረውና መፅሔቶችን የሚዘጋው ስጋት ስለፈጠሩበት ላይሆን ይችላል።
እናም፤ መፅሔቶቹ በየሕትመታቸው የሚፅፉት፣ መረጃ ለማሰራጨት፣ “ሕዝቡ”ን ለማሳወቅ፣ ለመልካም ለውጥ ለማነሳሳትና ለመቀስቀስ ቢሆንም፤ “ተችተውኛል፣ ፓርቲው የማልፈልገውን መረጃ ያሰራጫሉ፣ ለመንግስት የማይጥም ሃሳብ ይፅፋሉ፣ ደፍረውኛል” በሚል ከማሰር አይመለስም እንበል። እሺ ይሁን። ግን፤ ይሄን ሁሉ በግላጭ የሚያየው የአገሪቱ “ሕዝብ”፣ ለእውነትና ለነፃነት የቆመው፣ ለፍትህና ለሰው ክብር ፍቅር ያለው “ስልጡኑ ሕዝብ”፣ መንግስትን በመገሰፅ “ተው” ይለዋል? ለመሆኑ፤ ከመነሻው “ሕዝቡን” ማነሳሳትና መቀስቀስስ ለምን አስፈለገ? መንግስት አምባገነን ቢሆንም፣ ሕዝቡ ይህንን ስለማያውቅና ስለማይገባው ይሆን? ወይስ ሕዝቡ የመንግስትን አምባገነንነት ቢያውቅም፣ ለእውነትና ለነፃነት ደንታ ስለሌለው፣ የእኔነት ክብር ስለራቀው ወይም በጣም ፈሪ ስለሆነ ቀስቃሽ ያስፈልገዋል? ያው ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሚሉት መንገድ ስንሄድም፤ “ሕዝቡ” ላይ (እኛው ላይ) ጣታችንን መቀሰራችን አልቀረም።
ለማለት የፈለግኩት ምንድነው? በአንድ በኩል፤ ኢህአዴግና መንግስት ራሳቸውን እንደ እንከን የለሽ በመቁጠር፤ የዚህ አገር ችግር በአራት በአምስት መፅሔቶች ላይ ለማሳበብ የሚያደረጉት ሙከራ ዋጋ የለውም። በሌላ በኩል፤ የብዙዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተቃራኒ ሙከራም አያስኬድም። ኢህአዴግ በአንዳች ምክንያት፣ በምርጫም ሆነ በአመፅ፣ ወይም በሌላ መንገድ ከስልጣን ቢወርድ፣ ኧረ እስከነጭራሹ ጥፍት ቢል እንኳ፣ ተአምረኛ ለውጥ አይመጣም። የአገር ኋላቀርነት በአንዳች ተዓምር ብን ብሎ አይጠፋም።

የኢህአዴግ አስቸጋሪ ባህሪዎች ትግሉን ውስብስብና እልህ አስጨራሽ አድርገውታል
ተቃዋሚ ፓርቲዎች መንግስት ለመሆን የሚያስችል ቁመና አልፈጠሩም
የኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)ን ከመሰረቱት አንጋፋ ፖለቲከኞች  አንዱ የነበሩት አቶ ሙሼ ሰሙ ባለፈው ሳምንት ከፖለቲካ ፓርቲ ራሳቸውን ማግለላቸውን አስታውቀዋል፡፡ ኢዴፓን ከ92 ዓ.ም ጀምሮ በህዝብ ግንኙነት ሃላፊነት፣ በዋና ፀሐፊነትና በፕሬዚዳንትነት ያገለገሉት አቶ ሙሼ፤ ከፓርቲያቸው መልቀቃቸውን ምክንያት በማድረግ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው በአገሪቱ ወቅታዊ ፖለቲካ ዙሪያ በስፋት  አነጋግራቸዋለች፡፡ በተለይም በተቃዋሚ ፓርቲዎች የፖለቲካ እንቅስቃሴ ዙሪያ፣ኢዴፓና እሳቸው ለአገሪቱ ስላበረከቱት አስተዋጽኦ፣ስለመጪው ምርጫ፣ ስለተከሰሱት የግል የፕሬስ ውጤቶች፣ ስለኢህአዴግ...እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን  ተጠይቀው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡


          ባለፈው ሳምንት ከፓርቲ ፖለቲካ ራስዎን እንዳገለሉና ለፓርቲዎ የመልቀቂያ ደብዳቤ እንዳስገቡ በይፋ አስታውቀዋል፡፡ ምክንያትዎን ቢያብራሩልን?
ከኢዴፓ ጋር ላለፉት 15 ዓመታት ቆይቻለሁ፡፡ በፓርቲው ውስጥ የአመራርነት ሚና ነው የነበረኝ፡፡ ሰነድ በማዘጋጀት፣ የፓርቲውን የፖለቲካ ፍልስፍናና አቅጣጫ በመቅረፅ---ስራ እሳተፍ ስለነበር ፋታ ኖሮኝ አያውቅም፡፡ የኢትዮጵያ የተቃውሞ ትግል ጫና የበዛበት ነው፡፡ በዚህ ቦታ በአንድ መስክ ተሰማርቶ መቆየት ቆም ብሎ ራስን ለመፈተሽና ለመገምገም ጊዜ አይሰጥም፡፡ የሄድኩበት መንገድ ምን ያህል ውጤታማ እንደነበረ፣ ከዚህስ ማህበረሰቡ ምን ተጠቅሟል---የሚለውን ለመረዳት ትንፋሽ መውሰድ ---- ራሴን ማረጋጋት አለብኝ ብዬ ወስኛለሁ፡፡ ከተቋማዊ አሰራር ወጣ ብዬ ራሴን መገምገም ፈልጌአለሁ፡፡
የኢትዮጵያ የተቃውሞ ትግል ውስጥ እንደ ባህል የተለመደ ነገር አለ፡፡ ሰዎች ሰሩም አልሰሩም፣ፋይዳ ኖራቸውም  አልኖራቸውም ተቃዋሚ ፓርቲ ውስጥ ዝም ብሎ የመቆየት ባህል፡፡ እየታገሉ መኖር ይቻላል፤ ነገር ግን ለመኖር ብቻ የሚኖርበት ሁኔታ አለ፡፡ እዚያ ፓርቲ ውስጥ መቆየቴ አንድ ቀን ለውጥ ይመጣና  የማገኘው ጥቅም ይኖራል ብለው የሚያስቡ አሉ፡፡ ወይንም ደግሞ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ይሻሻልና ሚናዬን ለመፈተሽ እድል ይሰጠኛል በሚል ሊቆዩ ይችላሉ፡፡
እኔ ግን በአንድ ፓርቲ ውስጥ እስከአለሁ ድረስ ስራዬን መስራት አለብኝ ብዬ አምናለሁ፡፡ የሚገባውን ሰዓትና ጊዜ ሰጥቼ ኃላፊነቴን መወጣት አለብኝ፡፡ አሁን ባለሁበት ሁኔታ የስራዬ ባህሪ፤ ለረዥም ጊዜ ባለማቋረጥ በትግሉ ውስጥ በመቆየቴ፤ የቆየሁባቸውም ጊዜያቶች በከፍተኛ አመራር ውስጥ  በመሆኑ----ቆም እንድልና ራሴን እንድመረምር አስገድዶኛል፡፡ ለእንጀራ የሚሰራ ስራም ቢሆን እኮ 15 ዓመት ይሰለቻል፡፡
የእርስዎን ከፓርቲ ፖለቲካ ራስን ማግለል አስመልክቶ አንዳንድ ወገኖች “መጪውን የ2007 ምርጫ ሽሽት ነው፤ ከፖለቲካ ጫና ራስን ለማግለል ነው” የሚል አስተያየት ሲሰነዝሩ ይሰማል…
ሰዎች ብዙ ነገር ሊሉ እንደሚችሉ እገምታለሁ። ቁምነገሩ ግን ከእኔ እምነትና አስተሳሰብ ጋር ነው ያለው፡፡ በአለፉት 15 የትግል ዓመታት ከተቃዋሚዎችና ከመንግስት በኩል የተለያዩ ጫናዎችን አሳልፌያለሁ፤ ታስሬያለሁ፤ ተሰድጃለሁ፡፡ ይሄን ሁሉ ጫና ተቋቁሜ መጥቻለሁ፡፡ ከ1997 ዓ.ም በኋላ ደግሞ ተቃዋሚው ኃይል የነበረው ጫና፣ ግፊት፣ ስም ማጥፋትና ዘመቻው እጅግ ከባድ ነበረ፡፡ በዚያን ጊዜም ቢሆን ሃሳቤን አልለወጥኩም። ጫናን የምፈራ ቢሆን ኖሮ ወደ ትግሉ አልመጣም ነበር፤ እነዚያን የጫና ዘመኖች ተቋቁሜ አላልፍም ነበር፡፡ በምርጫ ወቅት የስራ ጫና ይበዛል፤ የሚያሳድረው ተፅዕኖም ቀላል አይደለም፡፡ በየአካባቢው ተሂዶ አባላት ከመመልመል ጀምሮ ቅስቀሳ እስከ ማድረግ ያለው ስራ ከባድ ነው፡፡ “እንደዚህ አይነት ከባድ ስራ አሁን መቋቋም ትችላለህ ወይ?” ብትይኝ፣ አሁን አልችልም። እረፍት እፈልጋለሁ፤ ትንፋሽ መውሰድ አለብኝ፤ ራሴንም ቆም ብዬ መገምገም ያስፈልገኛል፡፡ እንደ ሀገራዊ ምርጫ ያለን የምርጫ ዘመቻ ለመምራት ጊዜ ያስፈልጋል፣ መረጋጋትን ---- አእምሮ ነፃ ሆኖ መዘጋጀትን ይጠይቃል።
ምርጫውን ሽሽት ነው የሚሉ ተሳስተዋል ማለት ነው?
በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት አምስት ጊዜ አገር አቀፍ ምርጫ ተደርጓል፤ በአራቱ ተሳትፌያለሁ፡፡ የተለየ የምርጫ ባህሪ የታየበት 1997 ዓ.ም ነው፡፡ የተለየ ባህሪ እንዲኖረው ያደረገው ትግሉ የሄደበት መንገድ የፈጠረው ችግር ነው፡፡ በፖለቲካው ታስሬበታለሁ፡፡ ከምርጫው ውጪ በነበረ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ታስሬያለሁ፣ ተሰድጃለሁ፡፡ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል ውስጥ ከዚህ በላይ ሊኖር አይችልም፡፡ መጪው ምርጫ እንደዚህ ቀደሙ አስቸጋሪና የተወሳሰበ ነው ብዬ አላምንም፡፡ በውጤቱም ቢሆን ብዙ ትርጉም ያለው ነገር ይገኝበታል ብዬ አላስብም፡፡ ተቃዋሚውም ኃይል በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ መንግስትን የሚገዳደርበት ጉልበት እየፈጠረ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ስለዚህ መጪው ምርጫ ለተቃዋሚው በጎ ነገሮች አያመጣለት ይሆናል እንጂ ችግር የሚከሰትበት ነው ብዬ አላምንም፡፡ የ2007 ዓ.ም ምርጫ ከእኔ ውሳኔ ጋር  ምንም ግንኙነት የለውም፡፡
አሁን ባሉት የኢዴፓ አመራሮች ፓርቲው በመጪው ምርጫ ውጤት ያመጣል ብለው ያስባሉ?
ሰዎች እንደየአቅማቸው የተለያየ ባህሪና አቋም ይኖራቸዋል፡፡ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቃሚ የሆኑ ሰዎች ይኖራሉ፡፡ አሁን ኢዴፓ ውስጥ ያሉት አብዛኞቹ አመራሮች ወጣቶች ናቸው፡፡ በትግል ተመክሮዋቸው ጠልቀው የሄዱ አይደሉም፡፡ ነገር ግን ሌሎች ጠንካራ ጐኖች አሏቸው። እኛ ስንጀምር ኢዴፓን ኢዴፓ ለማድረግ ትልቁ ጉልበታችን ወጣቶች መሆናችን ነበር፡፡ አሁን አርጅተናል ማለቴ አይደለም፡፡ ሰርተን አይደክመንም፤ ሀሳባችንን በሰዎች ዘንድ ለማስረፅ አንታክትም፡፡ ያ የፓርቲያችን ጠንካራ ጎን አሁንም ኢዴፓ ውስጥ አለ፡፡ አሁን ፓርቲው ውስጥ ያሉት ልጆች እየተማሩ ያሉ ናቸው፡፡ በሚኖሩበት አካባቢ እና በማህበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ልጆች ናቸው። የእኛን ዓይነት ተመክሮ ላይኖራቸውና አጋዥ ኃይል ላይሆናቸው ይችላል፡፡ ይሄ አስቸጋሪም ቢሆን መታለፍ ያለበት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ በሰው ላይ እየተማመኑ ፖለቲካ ማራመድ አይቻልም፡፡ እያንዳንዱ ሰው ትግሉን እየተገዳደረ እያሸነፈ፣ እየሰበረ፣ እየለወጠ መሄድ አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ሊቸገሩ ይችላሉ፤ ችግሩ ግን የትግሉ አካል ነው፡፡ አቅማቸውን ለማጠናከርና ለማጎልበት ጥረት ማድረግ አለባቸው፡፡ ያለው ተጨባጭ ሁኔታም ያግዛቸዋል፡፡ ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ቅሬታ የሰላ ነው፡፡ ማህበረሰቡ ለኢህአዴግ ያለው እምነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸረ መጥቷል። ድህነት፣ ረሃብ፣ ስራ አጥነት፣ የአገልግሎት እጦት፣ የትራንስፖርት ችግር--- እነዚህ ሁሉ ቅራኔዎች በቅጡ ከተያዙና ከተጠቀሙባቸው ሌላ ተጨማሪ  መታገያ  ያስፈልጋቸዋል ብዬ አላምንም፤ እናም ለውጤት ብዙ ሩቅ አይደሉም፡፡
 “ሶስተኛ አማራጭ” የሚለው የፓርቲው ስትራቴጂ አሁንም ቀጥሏል?
ሶስተኛ አማራጭ የፓርቲው መሰረታዊ አቋም ነው፡፡ ይሄን አቋም የሚሸረሽርበት፤ አስተሳሰቡን የሚለውጥበት ምክንያት ይኖረዋል ብዬ አላምንም፡፡ እስካሁን ካለኝ ተመክሮ ለኢዴፓ የተለየ ዋጋ ከሚያሰጡት ነገሮች አንዱና ሊደርስበት ላሰበው ግብ እንደ ትግል ስልት የሚጠቅመው መንገድ ይሄ ብቻ ነው ብዬ ነው የማምነው፡፡ ከዚህ በተረፈ እኔ የምወስነው ጉዳይ አይደለም፡፡ አሁን እኔ ኢዴፓ ውስጥ አይደለሁም፤ ኢዴፓ ውስጥ ያሉ ሰዎች “ለትግል የሚያዋጣን ስልት ይሄ ነው” ብለው እስከአመኑ ድረስ ይቀጥሉበታል፡፡ ይሄ የእነሱ ውሳኔ ነው የሚሆነው።
በ15 ዓመት የትግል ዘመንዎ፣ ለኢትዮጵያ ምን አበረከትኩ ብለው ያስባሉ?
ትልቁ ነገር ኢዴፓን መመስረታችን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ኢዴፓ ፓርቲ እስከሆነበት ጊዜ ድረስ የህብረ ብሄራዊ አስተሳሰብና አጀንዳ እጅግ የተዳከመበት ጊዜ ነበር፤ ህብረ ብሄራዊነት የሚያዋጣ የትግል ስልት እንደሆነ አምነን፤ ህዝቡንም አሰባስበን ለሚፈልገው ግብ ለማድረስ፣ አደረጃጀትን በዚህ መንገድ መቀየድ ጥሩ ነው የሚለውን ነገር እንደ አስተሳሰብ በህብረተሰቡ ውስጥ እንዲሰርፅ ማድረጋችን ትልቁ ድላችን ነው፡፡ በዚያን ወቅት በህብረ ብሄራዊ አስተሳሰብ የተደራጀ ማንም አልነበረም፡፡ ለረዥም ጊዜ በህብረ ብሄራዊነት መደራጀት ተቀባይነት የሌለው አስተሳሰብ ሆኖ የቆየበት ጊዜ ስለነበር፣ ያ ትልቁ አስተዋፅኦዬ ነው እላለሁ፤ እንደ ድርጅት፡፡
ሰላማዊ ትግል ብቸኛው አማራጭ መሆኑን፣ በሰላማዊ ትግል ውስጥም ህገ መንግስቱን ማክበርና ልዩነቶችን በግልፅ አውጥቶ መታገል እንደሚቻል… ይሄን አስተሳሰብ በተቃዋሚ ፓርቲዎችና በህዝቡ ውስጥ ማስረጽ ችለናል፡፡ እኛ ወደ ትግሉ ከመምጣታችን በፊት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአብዛኛው ህገ መንግስቱን የሚያዩበት መንገድ የተዛባ ነበር፡፡ ህገ መንግስቱን ያለመቀበል (አንዳንዶቹ እንደውም ቀዶ መጣል ነው የሚል አስተሳሰብ ነበራቸው) ሁኔታ ይታይ ነበር፡፡ ያንን ሁሉ ማሸነፍ ችለናል ብዬ አምናለሁ፡፡ ያ ደግሞ ትልቁ አስተዋፅኦ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ በኢትዮጵያ የተቃውሞ ትግል ውስጥ በበርካቶቹ ዘንድ የተለመደው መፈክር ነበር፡፡ ብዙዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ርዕዮት ዓለም፤ የፖለቲካ ፍልስፍና አልነበራቸውም፡፡ የፖለቲካ ፍልስፍናን በኢትዮጵያ የተቃውሞ ትግል ውስጥ አስተዋውቀናል፡፡ ማስተዋወቅ ብቻ አይደለም፤ ቀላል የማይባሉ ሰነዶችን አዘጋጅተናል፡፡
የፓርቲውን ፕሮግራም፣ በብሄራዊ እርቅ፣ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ---ወዘተ አምስት ጥራዝ ሰነድ አዘጋጅተናል፡፡ ከዚያም በተከታታይ ሰፊ ሰነድ አዘጋጅቷል ኢዴፓ፡፡ ቀደም ሲል ትግሉን የሚመሩት አስተሳሰቦች ሳይሆኑ መፈክሮች ነበሩ፡፡ ዛሬ ሁሉም የተቃዋሚ  ፓርቲዎች የፖለቲካ ርዕዮት አለም ሰነዶች አሏቸው፡፡ ሌላው ኢዴፓ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ  ያስተዋወቀው ለምርጫ ክብር መስጠትን ነው፡፡ በሰላማዊ ትግል ውስጥ ምርጫ ብቸኛው የስልጣን ማግኛ መንገድ እንደሆነ በማያሻማ መልኩ በተቃዋሚው ዘንድ እንዲሰርፅ አድርገናል፡፡ ለምርጫ የሚመጣ ማንኛውም ኃይልም አማራጭ ሃሳብ ይዞ እንዲመጣ (ማኔፌስቶ እንዲያዘጋጅ) አነቃቅተናል፡፡ የመጀመሪያ የማኔፌስቶ ባለቤት ኢዴፓ ነው፡፡ ለቅንጅትም ማኔፌስቶ ያበረከትነው እኛ ነን። ፈፅሞ የተዘነጋውና ትርጉም የለውም ተብሎ ይቆጠር የነበረውን የባህር በር ጥያቄ  ዛሬ የሁሉም ፓርቲዎች መፈክር ማድረግ ችለናል፡፡ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ፒቲሽን አስፈርመን ለተባበሩት መንግስታት አቅርበናል፡፡ ውጤቱ ምንድን ነው ብለሽ እንዳትጠይቂኝ፡፡
ከ1997 ዓ.ም የምርጫ ጊዜ በኋላም ትግሉ አደጋ ደርሶበት በነበረበት ጊዜ ማህበረሰቡ ቆም ብሎ ጉዳዩን እንዲያጤን፣ በስሜት ሳይሆን በምክንያት እንዲታገል ሶስተኛው አማራጭን እንደ ሀሳብ ፓርቲው ይዞ መጥቷል፡፡ እነዚህ የጠቀስኩልሽ ነገሮች በሙሉ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የእኔ አሻራ አለባቸው፡፡
ቀጣዩ ምርጫ በ97 ዓ.ም. ከነበረው ምርጫ ጋር ሲነፃፀር ሊሰጠው የሚገባውን ግምት ሊገልጹት ይችላሉ?
በአሁኑ ጊዜ ያሉ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ አሸንፈው ስልጣን የሚይዙ ናቸው ብዬ አላምንም፡፡ ኢህአዴግን ግን ሊገዳደሩት ይችላሉ። በርከት ያለ ቁጥር አግኝተው ተወካዮች ምክር ቤት የመግባት እድል ሊኖራቸው ይችላል፡፡ በተረፈ ግን በተጨባጭ መንግስት ለመሆን የሚያስችል ቁመና አልፈጠሩም፡፡ ግልፅ ነው፤በቂ ህዝብ በደጋፊነት ማሰለፍ አልቻሉም፡፡ ኢህአዴግም ብዙዎች እንደሚያወሩት ዝም ብሎ ለጥቅማቸው፣ ለሆዳቸው፣ ለጊዜያዊ ፍላጎታቸው ያደሩ ሰዎች የተሰበሰቡበት አይደለም፡፡ እንደ ድርጅት በእምነት የሚከተሉት ቀላል የማይባል አባላቶች አሉት። የሚደረገው ውድድር ዝም ብሎ በአየር ላይ ካለ ድርጅት ጋር አይደለም፡፡ ውድድሩ በደንብ በህዝቡ ውስጥ መደላደል ይዞ ከሚንቀሳቀስ ድርጅት ጋር ነው። በፋይናንስ፣ በሰው ሃይል አቅም… መንግስት በመሆኑ ከሚፈጥረው ተፅዕኖ አኳያ በቀላሉ ልታሸንፊው የምትችይው ፓርቲ  አይደለም፡፡
ከዚህ አኳያ ተቃዋሚዎችን ስታይ ደግሞ በተቃራኒው ነው፡፡ በሰው ሃይል ሲታዩ በተደጋጋሚ ተመሳሳይ አመራሮች የሚታዩበት እውነታ ነው ያለው፡፡ የተለያዩ ሰዎች በተለያዩ ጊዜ በቅለው ሲጎለብቱና ሲጠነክሩ አናይም፡፡  ሁሌም የተለመዱ ፊቶች፣ ሰዎች፣ አመራሮችን ናቸው ያሉት፡፡ ከአንዱ ፓርቲ ወደ አንዱ ፓርቲ ሲሄዱ ነው የምናው፡፡ ይሄ አንደኛው የድክመታቸው መገለጫ ነው፡፡ በአብዛኛው ከተማ ተከል ናቸው፡፡ ከአዲስ አበባና ከክልል ከተሞቹ ውጭ ገጠር ሄደው አርሶ አደሩን በቅጡ መድረስ የቻሉ አይደሉም፡፡ ለዚህ  ምክንያት ሊደረደር ይችላል፡፡ አብዛኛው ማህበረሰብ በገጠር የሚኖር እንጂ በከተማ የሚኖረው 15 ፐርሰንቱ ነው። አጠቃላይ የከተማው 15 ፐርሰንቱ ቢደግፋቸውም እንኳን በምርጫ ሊያመጡት የሚችሉት ነገር የለም፡፡ እነዚህ ሃይሎች ለዚህ ያበቃቸው መሰረታዊ ምክንያት በ1997 ዓ.ም. የተፈጠረባቸው ችግር ነው ከተባለ--- አዎ። በርግጥ ብቸኛው ምክንያት አይደለም፡፡ አብዛኞቹ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአፈጣጠራቸው ችግር አለባቸው፡፡ በውስጣቸው ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ በደንብ ሰርጽዋል  ብዬ አላምንም፡፡ በምርጫ ሲወርዱና ሰዎች ሲተኩ አናይም፡፡ በውስጣቸው ዲሞክራሲ ያላበበ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ለህዝብ ዲሞክራሲ ለመስጠት ዝግጁ ናቸው ብሎ የሚያምናቸው የለም፡፡ ከባህሪም አኳያ ስታይው እየተካሄደ ያለው ትግል የአስተሳሰብ የበላይነትን ከመፍጠር ይልቅ የአርበኝነት መንፈስ ያየለበት ነው፡፡ የምናየው ኢህአዴግን ለመጣል የሚደረግ ትግል እንጂ አስተሳሰብን በህዝቡ ውስጥ አስርጾ መንግስት ለመሆን የሚያስችል አቅም ወይንም አቋም አይደለም፡፡ በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ኢህአዴግ እንዲወድቅ መመኘት ብቻ ነው፡፡ በርዕዮት ዓለም አለምም ደረጃ ጠንከር ጠብሰቅ ብለው የሚሰሩ ነገሮች አይታዩም፡፡ እነዚህ እነዚህ ሁሉ ከመነሻቸው ድክመቶቻቸው ናቸው፡፡
በ1997 ዓ.ም. የተፈጠረው ችግር ደግሞ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች በህዝብ ዘንድ የነበራቸውን እምነት እንዲያጡ አድርጓል፡፡ መከፋፈሉ፣ የተፈጠረውን እድል መጠቀም አለመቻላቸው፣ በኋላም ከእስር ቤት ወጥተው ራሳቸውን አጎልብተው በብቃት አለመራመዳቸው ---- ህዝብ የነበረውን እምነት ጥርጣሬ ላይ ጥሎታል፡፡
በዚህ ሁሉ ሂደት የኢህአዴግ አስተዋጽኦ ምንድነው?
የኢህአዴግን ችግርን ማየት ይቻላል፡፡ ኢህአዴግን እንደ ድርጅት ሳየው አንድ የተለየ ተልዕኮ ይዞ እንደመጣ ተዓምር አድርጐ ነው ራሱን የሚያስበው፡፡  ይሄንን የሚደግፈው ደግሞ ሰማዕታትንና የተከፈለውን መስዋዕትነት በመጥቀስ ስለሆነ፣ የአስተሳሰብ የበላይነትን ለመቀበል የተዘጋጀ ድርጅት አይደለም፡፡ ስለዚህ ለረጅም ዘመን በስልጣን ላይ ለመቆየት ሲል ማንኛውም ተፅዕኖ ያደርጋል፡፡ ቀድሞ ግብ አስቀምጦ፣ ከግቤ ከመድረሴ በፊት ማንኛውንም ሃይል መታገስ አልችልም ብሎ የሚያምን ድርጅት ነው፡፡ ምርጫ ይካሄዳል፡፡ ምርጫ  ማድረግ ብቻውን ግን አንድን አገር ዲሞክራሲያዊ አያስብላትም፡፡ የምርጫ ውጤትም ትርጉም አለው፡፡
መንግስት በተቃውሞ ትግል ውስጥ ያለው ሚና መንግስት እንደ ኢህአዴግ፤ ኢህአዴግ እንደ ኢህአዴግ ማየት ይቻላል፡፡ መንግስት ብዙ ጊዜ መንግስትነቱና ኢህአዴግነቱ ይምታታበታል፡፡ የዚህ ስርዓት ፈጣሪም ባለቤትም ስለሆነ፣ ይሄ ስርዓት በሌላ አስተሳሰብ ተፈትሾ፣ ከስልጣን ወርዶ ስለማያውቅ ስርዓቱንና ኢህአዴግን መንካት አንድ ሆነዋል፡፡ ስርዓቱን ስትታገይ ኢህአዴግን መታገል ነው፤ ኢህአዴግን ስትታገይ ስርዓቱን መታገል ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች እየተፈራረቁ በመጡበት ሁኔታ መቼም ቢሆን የአስተሳሰብ ለውጥ በአገሪቱ ውስጥ እንዲሰርፅ አያደርግም፡፡  የኢህአዴግ አስቸጋሪ ባህሪዎች ትግሉን ውስብስብ፣ በጣም አድካሚና እልህ አስጨራሽ አድርገውታል፡፡
ስለ ህዝቡስ አስተያየትዎ ምንድነው?
ህዝቡም ጋር ስትመጪ ቀላል የማይባል ችግር አይደለም ያለው፡፡ ህብረተሰቡ ለፖለቲካ ያለው ዝንባሌ በፍርሃትና በስጋት የተሞላ ነው፡፡ የትግሉ ባለቤት መሆን አልቻለም፡፡ ከተቃዋሚዎች የሚቀርብበት ወቀሳ ሊኖር ይችላል፡፡ የማህበረሰቡ ንቃተ ህሊናና ለመረጃ ያለ ቅርበት በራሱ ችግር ነው፡፡ ትግሉ በእነዚህ መንገዶች በማይታገዝበት ሁኔታ የተቃዋሚዎች ሚና ደካማ መሆኑ አይቀርም፡፡ ተቃዋሚዎች ተጨባጭ ሁኔታው የማይፈቅድላቸው ነገር አለ፡፡ ስራውን ለመስራት የሚያስችል በቂ ምህዳር የለም፡፡ ከኢህአዴግ በኩል ያለው ተፅዕኖ በጣም ከባድ ነው፡፡ ማህበረሰቡ ውስጥም ራስን የትግሉ ባለቤት አድርጎ የሚገኘውን ጥቅም ለመጋራት በቂ ተነሳሽነት አታይም፡፡
የተቃዎሚ ፓርቲዎች ወዲያው ተዋህደው ወዲያው መከፋፈል፤ እርስ በርስ መወነጃጀል…  ህብረተሰቡን ተስፋ አያስቆርጠውም ይላሉ?
በፖለቲካ አስተሳሰብ ዙሪያ ካልተሰባሰብሽ ጥላቻ ፖለቲካ ሊሆን አይችልም፡፡ ጥላቻ ሊወስድ የሚችለው መንገድ አለ፡፡ ኢህአዴግን መጥላት ብቻ በራሱ በቂ ርቀት ሊወስድ አይችልም፡፡ ፍልስፍና ሆኖ፣ የሰው ልብ ገዝቶ ትግልን ሊያጎለብትና ሊያጠነክር አይችልም፡፡ የመቻቻል፣ እውቅና የመስጠት፣ የተሞክሮ አለመኖር፣ የድርጅታዊ ብቃት ማነስ፣ የስልጣን ጥም---- እነዚህ ሁሉ የሚጫወቱት ሚና አለ፡፡ ከፖለቲካ ፍልስፍናው ውጪ፡፡ በአስተሳሰብ ዙሪያ ስትሰባሰቢ እምነትሽ አስተሳሰብ ይሆናል፡፡ ማንም ያንን አስተሳሰብ ቢያራምደው የአስተሳሰብ ባለቤት እስከሆንሽ ድረስ ችግር አይኖርብሽም፡፡ ሲጀመር የጠራ አስተሳሰብ አይደለም ያለው፡፡ ሁሉም የራሱን አስተሳሰብና እምነት በበላይነት ማራመድ ስለሚፈልግ ሽኩቻው የማያቋርጥ ነው የሚሆነው፡፡ ኢዴፓ ውስጥ ጥሩና ጠንካራ የምለው አስተሳሰባችን የጠራ መሆኑ ነው፡፡ እኛ ግለሰብ ላይ ሳይሆን በአስተሳሰባችን ላይ ነው የምናተኩረው። ቦታው ላይ በተቀመጠው ሰው ችግር የለብንም፡፡ በፓርቲ ውስጥ ክፍፍል የሚያመጡት እነዚህ ናቸው፡፡ በውስጣቸው በርካታ ችግር አለ፡፡ ፖለቲካ በትምህርት የሚመጣ ነገር አይደለም፡፡ በተግባር፣ በተሳትፎ ነው ፖለቲካን ማጠናከርና ማዳበር የሚቻለው። ድርጅት የሚጠነክረውና የሚጎለብተው በተሳትፎ ነው፡፡ ጥሩ ጥሩ ሰዎች ስለተሰበሰቡ አይደለም ፓርቲ ጠንካራ የሚሆነው። ፓርቲ በሂደት ነው ሙሉ የሚሆነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓቱ፣ የተቃውሞ ፖለቲካ ዕድሜው እና ተመክሮው አጭር ነው፡፡ የሚፎካከሩት ድርጅት ደግሞ ያለው ተሞክሮ ቀላል አይደለም፤ የስርዓቱ ባለቤትና ፈጣሪውም ነው፡፡ ስለዚህ ለተቃዋሚዎች ፈተና ነው፡
በቀጣዩ ምርጫ እንደ ተቃዋሚ ወይንም እንደተፎካካሪ  ኢህአዴግን ሊገዳደረው የሚችል ተቃዋሚ ፓርቲ አለ ብለው ያስባሉ?
እኔ ኢዴፓ ነው፣ ነው የምለው፡፡ ኢዴፓ ውስጥ ስላለሁ አይደለም፡፡ ኢህአዴግ የምርጫ ስርዓቱን ዴሞክራሲያዊ ካደረገው፣ የሚዲያ ተጠቃሚነትን ከፈጠረ፣ ሃሳቦች በደንብ እንዲንሸራሸሩ ሁኔታዎችን ካመቻቸ፣ ሰዎችን ማፈናቀሉን ካቆመ፣ ኢህአዴግን በአስተሳስብ በመገዳደር ብቁ ነው ብዬ የማስበው ድርጅት ኢዴፓ ነው፡፡ የጠራ የጠነከረ አስተሳሰብና አመለካከት ያለው ኢዴፓ ነው፡፡
በቅርቡ የተከሰሱ የግል የፕሬስ ውጤቶች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ጋዜጠኞችም ሃገር ጥለው ተሰደዋል፡፡ መጪው ምርጫ ነው----
ከትጥቅ ትግሉ በኋላ ለመጀመሪያዎቹ ሶስትና አራት አመታት በህዝቡ ዘንድ ኢህአዴግ ታማኝነት የነበረው ድርጅት ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን በህዝብ ላይ ያለው እምነት ሁልጊዜ በጥያቄ የተሞላ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት አማራጭ ሃሳቦች አንዲጎለብቱና እንዲዳብሩ አይፈልግም፡፡ እናም ማድረግ የሚችለው መረጃዎች ወደ ህዝብ የሚደርሱበትን ድልድዩን ማጥፋት ነው፡፡ የግል ጋዜጦች፣ መጽሔቶች ላይ የሚደርስባቸው ቅጥቀጣ እነሱ የተለየ አስፈሪ ስለሆኑ አይደለም፡፡ በማህበረሰቡና በአስተሳሰቡ መሃል ድልድይ በመሆናቸው ነው፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ እነሱ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ድልድዩን ለመስበር ነው፡፡ ህዝብ ባወቀ በነቃ በተደራጀ ቁጥር እንደሚፈታተነው ያውቃል። ህዝቡን ያወናብዱብኛል፣ ህዝቡን ያሳስቱብኛል፣ እኔ ከምፈልገው መንገድ ያስወጡብኛል የሚል ስጋት አለው። ስለዚህ የህዝብ ልሳን፣ አንደበት  ሆነው በማገልገል ላይ ያሉትን ጋዜጦች፣ መጽሔቶች ያዳክማል፡፡
አሁን በቅርቡ መጽሄቶች ላይ የደረሰው ነገር ለእኔ ግልጽ ነው፡፡ ኢህአዴግ አለማቀፍ ተጽዕኖውን አይፈልግም፤ ምክንያቱም ተበዳሪ መንግስት ነው፡፡ በተለያዩ መልኩ የሚደርሱበትን ተፅዕኖዎች ከወዲሁ ለመቋቋም እቅድ አድርጎ ኢህአዴግ የወሰደው የሚመስለኝ፣ የክስ ቻርጁን በግላቸው ከመስጠትና ከማሰር በፊት በቴሌቪዥን እንደ ቀይ ሽብር ማወጅ ነው፤ እናም ተነስተው ይጠፉለታል፡፡ ከዚያ ተገላገልኩ ነው የሚለው፡፡ ሙከራው በከፊል ተሳክቷል፡፡ ጋዜጠኞቹ ጥለው እየሄዱ ነው፡፡ በአዋጅ መልክ ክስ ከቀረ 23 ዓመቱ ነው፡፡ ደርግ ነበር ይሄን ያደርግ የነበረው፡፡ እነዚህ መጽሔቶች በብዙ አቅጣጫ ከፋይናንስ፣ ከአደረጃጀት፣ ከሰው ሃይል አኳያ ቀላል የማይባል ጉልበት የፈጠሩ ናቸው፡፡ ባለፈው አምስት ዓመት እንዴት  ህትመታቸው፣ ስርጭታቸው፣ እንደሚጎለብትና እንደሚጠነክር ያውቃል። እነዚህን ማዳከም ነው የያዘው፡፡ በእነሱ ምትክ አዲስ ጋዜጣ ያስገባል፤ አቅማቸው ደካማ ነው፣ እየተቆራረጡም እየተንጠባጠቡም ነው የሚቀጥሉት፡፡ በበቂ ደረጃም ህዝቡን አይደርሱም፤ ይቆማሉ፡፡ ስለዚህ ቀጣይነት፣ ወጥነት፣ ተከታታይነት ባለው መንገድ የሚታገሉትን መጽሔቶች ነው እንዲሰደዱ ወይም ፍርድ ቤት እንዲቆሙ ያደረገው፡፡ ይሄ ምርጫው ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ከመፈለግ ውጭ አይደለም፡፡  ሰው ይወናበዳል፣ ተወናብዶ እኔን አይመርጠኝም፤ የሚል ስጋትና ጥርጣሬ ስላለው ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ኢህአዴግ ከእሱ ቁጥጥር ውጪ የሆነ ማንኛውም ሃሳብን ለማራመድ የሚያገለግል መሳሪያ የሚፈልግ አይመስለኝም፡፡ እንደ እኔ አስቡ፣ እንደ እኔ ገምቱ የሚለው ደግሞ አያስኬድም፡፡
በዓለም ላይ የየሀገሩ ስጋት ተብለው የሚጠቀሱ የሀይማኖት፣ የዘር፣ የአምባገነናዊ ስርዓቶች አሉ፡፡ የኢትዮጵያ  ስጋት የትኛው ነው?
ሰዎች በተፈጥሮዋቸው አማራጭ ይፈልጋሉ፤ መፈለግ ብቻ ሳሆን አማራጭንም መፈተሽ ይሻሉ፡፡ አንድ መንግስት ለረዥም ጊዜ እንዲገዛቸው ፈቃደኛ አይደሉም፤ ይሰለቻሉ፡፡ ሰው ስሜቱን፣ ሃሳቡን፣ ፍላጎቱን እንዲያወጣ፣ እንዲገልጽ የሚያደርጉት ጋዜጦች፣ መጽሔቶች ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች በተዳከሙ ቁጥር በሰው ውስጥ ያለውን ነገር ለማወቅ እንዴት ይቻላል? ይሄ ደግሞ ወደ አመጽ፣ ወደ አለመረጋጋት ለመለወጥ የማንንም ይሁንታ አይጠብቅም፡፡ በደህንነትና በስለላ መዋቅር የሚቆም አይደለም፤ እንደ ጋዜጦችና እንደ ፓርቲዎች፡፡ ፓርቲዎችን አመራሮችን ሰብስቦ አስሮ፣ ትግሉን ማዳከም ይቻላል፡፡ በህዝብ ውስጥ ያለ ቁጣና ብስጭትን ግን መቆጣጣር አይቻልም፡፡ አንዳንዴ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታዩ ግጭቶች የዚያ ውጤት ናቸው ብዬ ነው የማስበው፡፡ ኢትዮጵያ እንደ ሃገር ችግር ይገጥማታል ብዬ አላስብም፤ ሊሆንም አይችልም፤ ሆኖም አያውቅም፡፡ ግን ስርዓቱ አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡ ስርዓቱ በዚህ መንገድ ያሉትንም እድሎች እያጠበበ፣ እየጨፈለቀ በሄደ ቁጥር ሰዎች  በውስጣቸው የሚቀጣጠለው ነገር የበለጠ እየጠነከረ እየጎለበተ ነው የሚሄደው፡፡ ጥያቄያቸው እያደገ ነው የሚመጣው፡፡ የተገኘውን እድል ተጠቅመው ፍላጎታቸውን ለማራመድ ወደ ኋላ አይሉም፡፡ ይህችን አገር ወደ መልካም አስተዳደርና ወደ ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ለመውሰድ ከተፈለገ፣ ተጨባጭ ሁኔታው በሚፈቅደው ልክ አሳታፊ የሆነ ስርዓት መገንባት ያስፈልጋል፡፡ ግዴታ ነው፡፡
ግብጽን ብናይ እስከ አሁን ድረስ መውጣት ባልቻለችበት የፖለቲካ ቀውስ እየታመሰች ነው ያለችው። ቀደም ብሎ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግብጽ ውስጥ በበቂ ሁኔታ ተደራጅተው፤ ትክክለኛ ቦታቸውን አግኝተው፣ ሃሳባቸውን ለመግለፅና ለማራመድ በሩ ክፍት ቢሆን ኖሮ፣ በአመጽና በህዝብ ቁጣ ሳይሆን በተቃዎሚ ፓርቲ ሃይሎች የስልጣን ሽግግር ሀገሪቱ ቀጣይነትዋን ታረጋግጥ ነበር፡፡ ህዝቡ ስሜቱን የገለጸው በምርጫ አይደለም፤ በአመጽ ነው፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መኖራቸው ጥቅሙ ህዝብ ፍላጎቱን በምርጫ እንዲገልፅ እድል ይሰጠዋል፡፡ ስለዚህ ለእኔ የሚታየኝ ስጋት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ መንገድ አልተሰራም፤ ልማት አልተካሄደም እያልኩሽ አይደለም፡፡ ስራ አጥነትን ለመቀነስ እንቅስቃሴ የለም፣ ማለቴ አይደለም፡፡ ግን በዚህች አገር ጉዳይ ያገባኛል ብሎ የተነሳ፣ የእኔ አማራጭ ነው የሚሻለው የሚልም አለ፡፡ ይሄ ሰው ሃሳቡ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ተደምጦ፣ በምርጫ ተሸንፎ ካልሆነ፣ በጉልበት በማፈን እንዳይራመድ ከተደረገ መጨረሻ ላይ ህዝቡ ውስጥ የሚፈነዳው  ሌላ ነገር ነው፡፡  

- የኢራናውያን አባል
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ የሰርከስ ትርዒት ይታይ ነበር፡፡ ከሰርከሱ ጋራ አንድ ግዙፍ ሰው ታየ፡፡ የትርዒቱ አካል ነበር፡፡
ይህ ግዙፍ ሰው አንድ ብርቱካን ያወጣና እንደ ጉድ ይጨምቀዋል - እስከመጨረሻው እንጥፍጣፊ ጠብታ ጨመቀው፡፡ ጉድ ተባለ ተጨበጨበ!
ከዚያ የፕሮግራሙ መሪ፤
“ይህ ታላቅ፣ ጡንቸኛና ጠንካራ ሰው ከጨመቀው በላይ ጨምቆ አንዲት ጠብታ ብርቱካን ጭማቂ ሊያወጣ የሚችል ሰው ካለ ወደዚህ ይምጣ?!” ሲል ጠየቀ፡፡
ሁሉም ፈራ፡፡
ቀጠለ የፕሮግራሙ መሪ፤
“እሺ አንድ ተጨማሪ ነገር ላክል - አንዲት ቅንጣት ላወጣ ሽልማት እሰጣለሁ፡፡ አንድ ሺ ዶላር!” አለ ጮክ ብሎ፡፡
ብረት በማንሳት የሚታወቅ ጉልቤ መንዲስ ጡንቸኛ፤ ወደ መድረኩ እየተጐማለለ መጣ፡፡ ከፕሮግራም መሪው የተጨመቀውን ብርቱካን ተቀበለ፡፡
ከዚያ ባለ - በሌለ - ጉልበቱ እንደ ጉድ እየጨመቀ፤
“እንዴት እንደምፈጠርቀው አሁን ታያላችሁ!” አለና በሁለት መዳፉ ደፈጠጠው፡፡
ግን ምንም ጠብ አላለለትም፡፡
ቀጠለና አንድ ግንበኛ ጡንቻውን ወጣጥሮ፤
“ይሄን ይሄንማ ለእኛ ተዉልን!” አለና ከብረት አንሺው ተቀበለ፡፡
ደጋግሞ ጨመቀው፡፡ አለው! አለው! ላብ - በላብ ሆነ! “ተሸንፌአለሁ” አለና ወረደ፡፡
“ሌላ የሚሞክር አለ?”  አለ የፕሮግራም መሪው፡፡
“አትችሉም! ያልኳችሁ ለዚህ ነው”
ከህዝቡ መካከል አንድ አጭር፣ ሲባጎ የመሰለ ኮስማና ከወደኋላ ብድግ አለ፡፡
“እኔ ልሞክር?” አለ፡፡
አገር ሳቀ፡፡ መሪውማ ዕንባው እስኪፈስ ነው የሳቀው፡፡ ሁሉ ሰው የመገላመጥ ያህል እየተገላመጠ አየው፡፡
ቀጫጫው ሰውዬ ግን በኩራት ራሱን ቀና አድርጎ በህዝቡ መካከል ሰንጥቆ ወደ መድረኩ ወጣ፡፡
“አመረርክ እንዴ?” አለው የመድረኩ መሪ፡፡
“አሳምሬ!” አለ ቀጫጫው፡፡
ቀጫጫው ብርቱካኑን መጭመቅ ሲጀምር ሳቁ ቀስ በቀስ ጋብ አለ፡፡
የሚገርም ነገር ተከሰተ፡፡ ወለሉ ላይ ጠብ ጠብ ማለት ጀመረ ብርቱካኑ፡፡
የፕሮግራሙ መሪ እጅግ በጣም በመደነቅ፤ “እንዴት ይሄን ተዓምር ልትፈጥር ቻልክ? አንተ ለራስህ ከአፍ የወደቀች ፍሬ የምታክል?” ሲል ጠየቀው፡፡
ቀጫጫውም፤
“አይ ጌታዬ እኔ የሂሳብ ሰራተኛ - አካውንታንት ነኝ!” አለው፡፡
*         *           *
ጎበዝ! ባገራችን የመጨረሻዋን ነጠብጣብ ጭማቂ ሂሳብ የሚያሰላ ሰው ባገኘን እንዴት በታደልን ስንቱ በተጋለጠ!  
ጉልበት እውነትን አይበልጥም! እርግጥ ጊዜያዊ ጡንቻ ዘለዓለማዊ ሀቅን ይበልጥ የሚመስለን ጊዜ ይኖር ይሆናል፡፡ ግን የዓለምን ታሪክ መለስ ብሎ ማየት ትልቅ ትምህርት ይሆነናል፡፡ ናፖሊዮን ቦናፓርት፣ ሪቻርድ ባለ አምበሳ-ልቡ (The Lion – hearted) ታላቁ እስክንድር፣ ጁሊየስ ቄሣር፣ ጄንጂስ ካሃን … ሁሉም ታላላቅ ነበሩ፡፡ ሁሉም “ከሸክላነት ወደገደልነት” ተሸጋገሩ፡፡ ‘መኳንንትም ሲሻሩ ህዝብ ናቸው’ እንዲል አንጋረ ፈላስፋ። አንድን ህዝብ ለመምራት ታላቅነት በምንም መልኩ ሀቀኛ መለኪያ አይሆንም! ታላቅነት ከየት ይመነጫል? ቢባል አንድና አንድ መለኪያ ብቻ የለውምና! ታላቅ ነኝ ብሎ ዘለዓለማዊነት የተጎናጸፈ የለምና … They mistook longevity for immortality ይሏልና፡፡ ረዥም ዘመንን ከዘለዓለማዊነት ጋር ያምታቱታል ነው ነገሩ!  
“የጾምነው ነገር ቢበዛም
መፈሰኪያው ቀን አይቀርም!”
ይላል አንድ ፆመኛ ገጣሚ፡፡ ዕውነት ነው፡፡ እንደሶስተኛው ዓለም ባለ አገር፤ ከፍስኩ ፆሙ ይበዛል። ዲሞክራሲን ከፈሰከው የፆመው ይበዛል፡፡ ፍትህን ካየው ያላየው ይበዛል፡፡ ሀቅን ካገኘው የፆመው ይበረክታል። መልካም መስተዳድርን ከተጎናፀፈው የተራቆተው ይበዛል፡፡ ዞሮ ዞሮ መፆም ተለምዶ ፍስክን አርቆ ማየት ልክ እየመሰለ መጥቷል፡፡ መንገድ ከመጀመራችን በፊት የመንገዱን እርቀት እንመትር ቢባል የሚሰማ ጠፍቷል - ከሁሉም ወገን! አንዴ “እናሸንፋለን”፤ ካሉ “ተነጋግረን እንስማማለን” “እንደሰለጠነ ሰው ተቀራርበን እንፈታዋለን” ማለት እርም ሆኗል፡፡ ስለአገር ምን አገባን”፣ “ስለህዝብ ምን አስጨነቀን?” ማለት ወግና ልማድ የሆነ ይመስላል - በተግባር የለምና!
ዛሬም ከሼክስፔር ጋር፣ በፀጋዬ ገ/መድህን አንደበት፤
“ዛሬ ለወግ ያደረግሽው፣ ወይ ለነገ ይለምድብሻል
ልማድ ፊት እንዳሳዩት ነው፣ ወይ ይጠፋል ወይ ያጠፋል  
ከርሞም የሰለጠነ እንደሁ፣ ተፈጥሮ ይሆናል ይባላል” ማለት ተገደናል፡፡
የክረምቱን ሰዓት ስናስተውል፤
“ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት
ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት”
መባሉ ጊዜን አመላካች ብቻ ሳይሆን ያለፈ ድርጊትን አመላካችና ለንጋትና ለመስከረም ዝግጁ መሆንንም ጠቋሚ ነው፡፡ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን እንደተምኔት ሳይሆን እንደተጨባጭ ነገር ማስተዋል ይገባናል፡፡ ፅንፍና ፅንፍ እየቆሙ፣ ማዶና ማዶ የጎሪጥ እየተያዩ፣ በደፈረሰ ልብ እያሰሉ፣ የምንመኘውን ዓይነት ለውጥ ማምጣት ከባድ ነው፡፡ ከቶውንም፤ በትንሹ የምንመኛቸውን ነገሮች እንኳ በእጃችን ማስገባት አዳጋች ይሆናል፡፡
የእንግሊዙ ፈላስፋ፣ መሪና ጠበቃ ፍራንሲስ ቤከን፤
“የምንፈልጋቸውና የምንጓጓላቸው ነገሮች ጥቂት፤ የምንፈራቸው ግን ብዙ ሲሆኑ፣ የአዕምሮ ደረጃችን ጎስቋላ ሆነ ማለት ነው” ይለናል፡፡
ግባችንን በውል ለመምጣት የእኛን መንገድ ብቻ “አንደኛ ነው!” የእነ እገሌ ውራ ነው” እያልን በአፈ ቀላጤዎቻችን ብናወራ ራስ-በራስ መሸነጋገል እንጂ ሁነኛ ፍሬ የሚያፈራ ጉዞ አይሆንም፡፡
ጆርጅ በርናርድ ሾው፣ አየርላንዳዊው ፀሐፌ-ተውኔትም “ሰው ነብርን ሲገል ስፖርት ነው ይለዋል፡፡ ነበር ግን ሰውን ሲገል ጭካኔ ነው ይባላል” ይለዋል፡፡ ዕይታችን “ወደ ገደለው” መሆኑ ነው፡፡
ምንጊዜም ሁሉም የየራሱን እንቅፋት መደርደሩ አይቀርም፡፡ በየዘመኑ የምናየው ነው፡፡ ዱሮ ቀኝ መንገደኞች፣ አምስተኛ ረድፈኞች፣ ፀረ-ህዝቦች፣ ሥርዓተ-አልበኞች፣ አስመሳዮች፣ አድርባዮች ወዘተ ይባል እንደነበር እናስታውሳለን፡፡  ይባል የነበረው በሀቅ ነው ወይ? ብሎ ጠይቆ አዎንታዊ ምላሽ ማግኘት ግን ዘበት ነው፡፡ ለሥልጣን መቆያነቱ ግን አያጠያይቅም፡፡ ኢራናውያን እንቅፋቶቻቸውን ሲደረድሩ በየዘመኑ የሚያቅን “የስብሰባ ጠላቶች - አልኮል፣ ኮሌስትሮል፣ ፕሮቶኮል፤ ናቸው” ይላሉ፡፡ እነዚህ እኛንም ሳይመለከቱን አይቀሩምና በጊዜ መጠንቀቅ ነው!!  

Published in ርዕሰ አንቀፅ
Page 6 of 20