የፊልም ባለሙያ በነበረው ሚሼል ፓፓታኪስ በተፃፈው“ይሄ ሁሉ ለምን” የተሰኘ መፅሀፍ ላይ ነገ ውይይት እንደሚካሄድ አዘጋጁ ሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ ገለፀ፡፡ ከቀኑ 8ሰዓት ጀምሮ በብሄራዊ ቤተ-መፅሀፍትና ቤተ-መዛግብት ኤጀንሲ አዳራሽ በሚካሄደው በዚህ ውይይት ላይ አቶ ገዛኸኝ መኮንን ለውይይት የሚሆን መነሻ ሃሳብ የሚያቀርቡ ሲሆን የንባብ ወዳጆች እንዲሳተፉና ሃሳብ እንዲያዋጡ በአዘጋጁ ጥሪ አቅርቧል፡፡

Saturday, 30 August 2014 11:03

የሎተሪ እጣው!

         የህይወት ትርጉም ምንድነው? በሚል እብከነከን ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ህይወት ትርጉም ኖራት፣ አልኖራት የራስዋ ጉዳይ! በሚል ትቼዋለሁ፡፡ ስለህይወት ሳይሆን ስለ ቁጥሮች ትርጉም ማሰላሰል ጀምሬያለሁ፡፡ በህይወት መኖራችንን የምናውቀው እድሜያችንን ስንቆጥር ወይንም በመንግስት ስንቆጠር ይመስለኛል፡፡ ይህን ታሪክ ያጫወተኝ ግለሰብ በ1999 ዓ.ም የህዝብ ቆጠራ፣ በመንግስት የመቆጠር የዜግነት ግዴታውን ተወጥቶ፣ 46 ዓመት ዕድሜ አስቆጥሮ ህይወቱ ካለፈ 7 ዓመት ተቆጠረ፡፡ ህዳር 1983 ዓ.ም ይመስለኛል፡፡ የመሥሪያ ቤታችን የሥራ ባልደረባ የአቶ አዱኛ በጡረታ መገለልን ተከትሎ በአለቃዬ ትዕዛዝ የሽኝት ፕሮግራም ለማዘጋጀት በየቢሮው እየዞርኩ ገንዘብ ማሰባሰብ ጀመርኩ፡፡ አብዛኛው ሰራተኛ ገንዘብ ለማዋጣት ፍቃደኛ አልሆነም፤ የተዋጣውም ገንዘብ እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም፡፡ የአቶ አዱኛ ከሰው የማይገጥም ጠማማ ባህሪ ለገንዘቡ ማነስ ዋናው ምክንያት ነበር፡፡ መልቲ፡፡

ማሽንክ፡፡ እኩይ፡፡ መሰሪ ቢሮክራት ነበሩ፡፡ ግንባራቸው ላይ የተነደለ፣ የተጠረመሰ ጠባሳ ታትሞበታል፡፡ በዚያ ሽንቁር እነ በጎነት፣ እነ ቅንነት፣… ተነው በነው ሳይጠፉ አልቀሩም፡፡ የተገኘውን መዋጮ በማብቃቃት ሁሉም ዝግጁ ሆነ፡፡ ሾካካነቷ እና ለወሬ ሟችነቷ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ተላላኪዋ የሺ ከጉድ ነው ያወጣችኝ፡፡ የጉልበት ልፋቷ ሳያንስ ከሰልና ስኳር ከገዛ ቤቷ ነበር ያመጣችው፡፡ … ወደ 10፡00 ሰዓት ገደማ የመ/ቤቱ ሥራ አስኪያጅና ተሰናባቹ አቶ አዱኛን ጨምሮ ወደ 30 ሰራተኞች ገደማ በአዳራሹ ታደሙ፡፡ የተጎዘጎዘው ቄጤማ፣ የቡናው መዓዛ… በዚያ ሰፊ ሙት አዳራሽ ላይ ሕይወት ዘሩበት፡፡ የጠቅላላ አገልግሎት ኃላፊው ዘነበ ፕሮግራሙን በማስተዋወቅ ላይ ነበር፡፡ ከየሺ ጋር ላይ ታች ስንባትት ዞር ብሎ ያላየን ሰውዬ ባለቀ ሰዓት የፕሮራሙ አጋፋሪ ሆኖ ቁጭ አለ፡፡ “…በመጨረሻም የማስታወሻ ስጦታ በማበርከት የፕሮግራሙ ፍፃሜ ይሆናል፡፡” ሲል ደመደመ፤ አጋፋሪ ዘነበ፡፡ እኔ ክው አልኩ፡፡ የምን የማስታወሻ ስጦታ? ትልቁ ዳቦ ሊጥ ሆነ! “ስለ ስጦታ የዝግጅቱ መርሃ ግብር ላይ አልተፃፈም፤ ከየት አምጥተህ አነበብከው?!” ስል ዘነበ ላይ ደነፋሁበት፡፡ “ሽኝት ካለ ስጦታ አይቀሬ ነው ብዬ ነው” ሲል መለሰልኝ፡፡ ሰው እንዴት በግምት ይናገራል? እርጉም! ከይሲ! በዚህ ሰዓት የማስታወሻ ስጦታ ከየት ሊመጣ ነው? በምን ገንዘብ? እንዴት? ብዙ አወጣሁ፤ አወረድኩ፡፡

ጠብ ያለልኝ ነገር ግን የለም፡፡ ፕሮግራሙ ቀጥሏል… ሻይ ቡና፣ ለስላሳው… ከበቂ በላይ ተዳርሷል፡፡ የማስታወሻ ስጦታውን ነገር ሳስብ እንደ አዲስ ደነገጥኩ፡፡ …አንደበተ ርዕቱው ዘነበ እንደተለመደው የውዳሴ ዲስኩሩን “ህይወት” ሲል ጀመረ፡፡ “ህይወት - ብልጭ ብሎ ድርግም እንደማለት ሁሉ ቅጽበት ነው፡፡ በዚያች ሽራፊ አፍታ እልልታ - በዋይታ … ሆታ - በእሪታ ይፈራረቃሉ… በዚህች ቅጽበት ሳቅም ለቅሶም አሉ፡፡ የሳቀው እንደሳቀ … ያለቀሰውም አንብቶ ሳይጨርስ ሁሉም ነገር ድርግም ይላል - ሞት!” ስለ ስጦታው ብልጭ ብሎ ድርግም የሚል ሐሳብ አእምሮዬ ውስጥ ፈነዳ፡፡ ሁሉም ነገር ድርግም እንዲል አዳራሹ መሐል መብረቅ ወድቆ ዶግ አመድ ቢያደርገን ተመኘሁ፡፡ የዓለም ፍፃሜ… የፕሮግራሙ ፍፃሜ--የማስታወሻ ስጦታ ፍጻሜ--- አዲዮስ! ዘነበ ዲስኩሩን ቀጥሏል “ትላንት ስለሕይወት ስንት ሲያቅዱ የነበሩ… ዛሬ በሞት መዳፍ ስር ያሉ የሥራ ባልደረቦቻችን አንዘንጋ፡፡ ለጡረታ ወግ ሳይታደሉ እንደዘበት ያጣናቸውን አንርሳ! …አቶ አዱኛ ለዚህ ወግ ማዕረግ እንኳን አደረሰዎት”… የፎቶግራፍ ፕሮግራም ቀጠለ…. ዲስኩረኛው ዘነበ “ይህቺ የጨረቃ ምሽት በሕይወታችን ውስጥ ተወርዋሪ ኮከብ ሆና እንድታልፍ ዝግጅቱን ላስተባበሩት ምስጋና ይገባቸዋል…” አይ ዘነበ! የጨረቃ ምሽት ተወርዋሪ ኮከብ ብሎ ነገር እኮ የለም፡፡ ያለነው እንደ ዋሻ ጨለምለም ብሎ የከብት በረት ገጽታ ባለው የመ/ቤት አዳራሽ ውስጥ ነው፡፡ ፕሮግራሙ በተያዘለት መርሀ ግብር ቀጥሏል፡፡ ወደ ፍፃሜውም ተቃርቧል፡፡

የፍፃሜ ጦርነት! ሹልክ ብዬ ልውጣ ይሆን? …በደመነፍስ የኪስ ቦርሳዬን አወጣሁ፡፡ ከሳምንት በፊት በቆረጥኩት የገና ስጦታ ሎተሪ ላይ አይኖቼ አረፉ፡፡ የገና ስጦታ፡፡ የማስታወሻ ስጦታ፡፡ ቢንጎ! ቁጥሮቹን እንደዘበት አየኋቸው - 44፡88 ይላሉ፡፡ በፖስታ አሽጌ ለስጦታ አዘጋጀሁት፡፡ ለዘነበ ሐቁን ነገርኩት፡፡ “አቶ አዱኛን በማይመጥን ለይስሙላ በሚበረከት ሙት ስጦታ ላይ ህይወት እንደምትዘራበት እምነቴ ነው፡፡” አልኩት፡፡ …ዘነበ ለጋ ቅቤ እንደዋጠ ሕፃን አንደበቱን አለዝቦ “… እነሆ የህይወት ወንዝ ጅረት አቶ አዱኛን ከጡረታ ደለል ላይ ጥሎአቸዋል፡፡ ለወርቃማ ቀሪ የአዛውንትነት ዘመናቸው ጽዋዬን አነሳለሁ፡፡ እኛ አበሾች፤ ለሞት የብፅአት፣ ለእርጅና የፀጋ ማዕረግ የምንሰጥ ምርጥ ህዝቦች ነን፡፡ ከስጦታው ባሻገር የሰጪው ምኞት በዚህ ፖስታ ውስጥ በፍቅር ታሽጓል፡፡ በሺህ የሚቆጠሩ ምኞቶች …ሙሉ የገና ስጦታ የሎተሪ ትኬት… የመ/ቤቱ ሥራ አስኪያጅ ስጦታውን ያበረክቱልናል፡፡”

አቶ አዱኛ ግር እንዳላቸው ፖስታውን ተቀበሉ፡፡ ፊታቸው ፍም መስሏል፡፡ ይህ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ስጦታ በመላ ሠራተኛው ዘንድ ግርምት አጫረ፡፡ በማሾፍ የገለፈጡ… በሟሽሟጠጥ አቃቂር ያወጡ ነበሩ፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ግን እንደ ዱብ ዕዳ የሚቆጠር ሰበር ዜና ተሰማ፡፡ ወሬው እንደተስቦ በሽታ ከቢሮ ቢሮ በፍጥነት ተዛመተ፡፡ አቶ አዱኛ ሰራተኛው ባበረከተላቸው የሎተሪ እጣ በሙሉ ትኬት የ25ሺ ብር አሸናፊ ሆኑ! አብዛኛው ሰራተኛ በቅናት እርር ድብን አለ፡፡ “እንዴት ሎተሪ ለስጦታ ታቀርባለህ? ሰይጣኑ አዱኛ ሊደርሰው ይችላል ብለህ መጠርጠር ነበረብህ!” የሚል መያዣ መጨበጫ የሌለው ወቀሳም ያቀረቡ ነበሩ፡፡ ለራሴ የቆረጥኩትን ሎተሪ ---- የራሴን እድል አሳልፌ መስጠቴን ማን አወቀልኝ! ምንስ ተብሎ ይወራል፡፡ እንደው ዝም፡፡ የእግር ውስጥ እሳት … ረመጥ! ህይወቴ ወደ ሰቅጣጭ ቅዥት ተለወጠች፡፡ 44.88 የሚሉ ቁጥሮች በእዝነ ሕሊናዬ ብልጭ ድርግም እያሉ ሰላም ነሱኝ፡፡ ከህሊናዬ የማይፋቁ …ለዝንተአለም በአእምሮዬ የታተሙ ምትሀታዊ ቁጥሮች! አንድ ሁለት …ስድስት ዓመታት እንደ ዘበት ተቆጠሩ፡፡ ዛሬም ቀኑ ትዝ ይለኛል፡፡ ሐምሌ 17 ቀን 1989 ዓ.ም …የጠቅላላ አገልግሎት ኃላፊው የዘነበ ሥርዓተ ቀብር ዮሴፍ ቤተክርስቲያን እየተፈጸመ ነበር፡፡ ሁሌም ዲስኩሩን “ሕይወት” በሚል የሚጀምረው አንደበተ ርዕቱ ዘነበ፣ በሞት ተለይቶ አፈር እየተመለሰበት ነው፡፡ የህይወት ወንዝ ጅረት ከጡረታ ደለል ላይ ሳይጥለው፣ ደለል አፈር እየተመለሰበት ሳለ ከለቀስተኛው መሐል አቶ አዱኛ ላይ አይኔ አረፈ፡፡ ምትሐት ሆነውብኝ ክው ብዬ ደነገጥኩ፡፡ ስርአተ ቀብሩ ተፈጸመ፡፡ አይኖቼን ከአቶ አዱኛ ላይ አልነቀልኩም፡፡ ወደ መ/ቤቱ ሰርቪስ ከሚገባው ለቀስተኛ ነጠል ብለው ቁልቁል ወረዱ፡፡ ተከተልኳቸው፡፡ ሐቁን መንገር አለብኝ፡፡

ምን ብዬ መጀመር እንዳለብኝ እያውጠነጠንኩ ከኋላ ስከተላቸው… ሳሪስ ካዲስኮ ህንፃ ጋር ዘወር ሲሉ አይን ለዓይን ግጥምጥም፡፡ ሞቅ ያለ ሰላምታ አቀረቡልኝ፡፡ ከአጀንዳዬ ውጭ ስለ ሟቹ ዘነበ ተጨዋወትን፡፡ መኖሪያ ቤታቸው ደጃፍ ላይ እንደደረስን ያወቅሁት በር ሲያንኳኩ ነው፡፡ “ቤቴን ካላየህ ሞቼ እገኛለሁ” ብለው በግድ አስገቡኝ፡፡ ጊዜ ሳላጠፋ ብሶቴን ተነፈስኩ፡ “እነዚያ ትኬቶች የእኔን ሕይወት ሊለውጡ ከአምላክ ተበረከቱልኝ፤ ግን…” ሳግ ተናነቀኝ፡፡ ማንባት ጀመርኩ፡፡ አቶ አዱኛ ግራ ገብቷቸው ትክ ብለው ያዩኛል፡፡ ሰከን አልኩ፡፡ ሁሉንም ተረጋግቼ አጫወትኳቸው፡፡ “ዛሬ ትርጉም ባይኖረውም ሐቁን ይወቁት” ብዬ----የሽኝት ፕሮግራሙ ላይ የተሰጣቸው ሎተሪ ለራሴ የገዛሁት እንደነበር ነገርኳቸው፡፡ “እኔም ሐቁን እነግርሃለሁ …አጉል እልህ ገብቼ” …አሉና ቡናቸውን ፉት አሉ፡፡ “በሥራዬ ራሴን የማላስደፍር ቆፍጣና ነበርኩ - በስመ ሽኝት የተሰጠኝ ስጦታ ግን እኔን ለማዋረድ የተሸረበ ሴራ አድርጌ ወሰድኩት …የሎተሪ ትኬት የያዘውን ፖስታ ስቀበል ያሽሟጠጡ፣ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው የገለፈጡም ነበሩ… በዚህም ስሜቴ ተንኮታኩቷል፡፡” “እናም እቅድ አወጣሁ---ብሔራዊ ሎተሪ በኃላፊነት የሚሰራ የቅርብ ሰው ነበረኝ… እሱ በሚያውቀው ጥበብ፣ የ25ሺ ብር እጣ ያሸነፍኩበትን ትኬት መግዛት ቻልኩ---- ለይስሙላ እንጂ ድንቡሎ ያላገኘሁበትን …አጉል እልህ ገብቼ…“ “የባሰ አታምጣ! ሎተሪው አልደረስዎትም ማለት ነው?” “በፍፁም!” ብለው አምባረቁ፡፡ በንዴት ቱግ እንዳሉ ብድግ ብለው ወደ ቁምሳጥኑ አመሩ፡፡ ቁምሳጥኑን ከፍተው የሆነ እቃ ይፈልጉ ጀመር… ውድ አንባቢያን፡- እኚህ መሰሪ፤ መጀመሪያ ላይ ሽጉጥ እየፈለጉ መስሎኝ በፍርሃት እርጄ ነበር፡፡ እሳቸው ግን …ዳጎስ ካለ አጀንዳ ውስጥ የሎተሪ ትኬት አውጥተው “ያንተ ሎተሪ ያውልህ!” አሉና ንዴት በተቀላቀለበት ስሜት ወረወሩልኝ፡፡ አገላብጬ አየኋቸው፡፡ የገና ስጦታ ሎተሪ! ቁጥሮቹ ላይ አይኔ እንደሙጫ ተጣበቀ - 44.88!!

Published in ልብ-ወለድ

ኪነጥበብ (Art) የሰው ልጅ ሁለንተናውን የሚነድፍበት፣ ስሜቱንና አመለካከቱን የሚቀርጽበት ዘርፍ ነው፡፡ ዲሲፕሊኑ እጅጉን ሰፊ የሆነና በውስጡም ብዙ ሙያዎችን (እንደ ሥዕል፣ ድርሰት፣ ተውኔት፣ ሙዚቃ፣ ቅርጻቅርጽ፣ ፎቶግራፍ፣ የፊልም ጥበብ…) የሚያቅፍ ሲሆን በርካታ ንድፈ ሀሳቦችን ከተለያዩ ሙያዎች በመውሰድ ራሱን የሚያበለጽግ መስክ ነው፡፡ ያም ሆኖ መስኩ ከባህልና ከፍልስፍና ጋር ያለው ቁርኝት እጅጉን የጠበቀ ነው፡፡ ኪነጥበብ በታሪክ፣ በርዕዮተ ዓለሞች መለዋወጥና በክስተቶች ውስጥ ትኩረቱና አገልግሎቱ ተለዋውጦአል፤ ይለዋወጥማል፡፡

           ዛሬ ስነ ጽሑፍን ማደሪያ አድርገን አቢይ ዘርፉ ስለሆነው ስነ ግጥም እንድናወራ ወደድኩ፡፡ የጽሑፌ ጉዳይ የአማርኛ ስነ ግጥም፣ ትኩረቱም ኪነጥበብን ጭብጣቸው (Theme) ያደረጉ “የታተሙ ግጥሞች” ናቸው፡፡ እናም መነሻዬን የ1950ዎቹ መግቢያ፣ መድረሻዬንም ያለንበትን አሰርት አድርጌ በየዘመኑ በተጻፉት ግጥሞች ላይ የኪነጥበብ ጭብጥ ምን ይመስላል? ገጣሚያኑስ ለኪነጥበብ የነበራቸው እይታ ምንድን ነው? የሚለውን እጅጉን ቁንጽል በሆነ ወፍ በረር ዳሰሳ ላስቃኝ፡፡ ጭብጥ (Theme) በአንድ ኪናዊ ሥራ ውስጥ አቢይ ጉዳይ ነው፡፡ ያለ ጭብጥ የተከየነ ጥበባዊ ሥራ አለ ለማለት ያስቸግራል፡፡ በግጥምም ውስጥ ጭብጥ ከግጥሙ ማዕከላዊ ሀሳብ (idea) ይሰርጻል፡፡ የአንድን ኪናዊ ሥራ ጭብጥ ማግኘት ብዙውን ጊዜ ቀላል አይደለም፡፡ በመሆኑም የግጥሙን ማዕከላዊ/ገዢ ሀሳብ በመረዳት ጭብጡ ይሄ ነው ለማለት ጥልቅ ንባብ፣ የቋንቋና የቃላት እውቀት አለፍ ሲልም የሌሎች ሙያዎች መጠነኛ እውቀት ያስፈልጋል፡፡ “የግጥም ሥራዎችን እንደሚያነሱት አቢይ ጭብጥ በልዩ ልዩ ጭብጣዊ ዘውጎች ማዋገን” ይቻላል፡፡ ይህም ጭብጥን በቅጡ ለመረዳት የተሻለ መንገድ እንደሆነ አጥኚዎች ይገልጻሉ፡፡

ኪነጥበብ (Art) የሰው ልጅ ሁለንተናውን የሚነድፍበት፣ ስሜቱንና አመለካከቱን የሚቀርጽበት ዘርፍ ነው፡፡ ዲሲፕሊኑ እጅጉን ሰፊ የሆነና በውስጡም ብዙ ሙያዎችን (እንደ ሥዕል፣ ድርሰት፣ ተውኔት፣ ሙዚቃ፣ ቅርጻቅርጽ፣ ፎቶግራፍ፣ የፊልም ጥበብ…) የሚያቅፍ ሲሆን በርካታ ንድፈ ሀሳቦችን ከተለያዩ ሙያዎች በመውሰድ ራሱን የሚያበለጽግ መስክ ነው፡፡ ያም ሆኖ መስኩ ከባህልና ከፍልስፍና ጋር ያለው ቁርኝት እጅጉን የጠበቀ ነው፡፡ ኪነጥበብ በታሪክ፣ በርዕዮተ ዓለሞች መለዋወጥና በክስተቶች ውስጥ ትኩረቱና አገልግሎቱ ተለዋውጦአል፤ ይለዋወጥማል፡፡ ከዚሁ ከኪነጥበብ የሚወለደው ስነ ጽሑፍም ከተለያዩ የሙያ መስኮች የተለያዩ ጽንሰ ሀሳቦችንና ንድፈ ሀሳቦችን ወስዶ በማልመድ የዳበረ ጥበብ ነው፡፡ የእሱ “ቀዳሚው ልጅ” የሆነው ስነ ግጥምም እንዲሁ፡፡ እንግዲህ አስቀድሜ እንዳልኩት ጉዳዬ ኪነጥበብን ጭብጣቸው ያደረጉ ግጥሞች ናቸው፡፡ ትኩረቴም የኪነጥበብ አንጋፋ ልጅ የሆነው ስነ ግጥም፣ “አባቱን” ኪነጥበብን ጭብጡ ሲያደርገው ምን ይመስላል? የሚለው ላይ ነው፡፡ 1950ዎቹ በኢትዮጵያ በየመስኩ በርካታ አዳዲስ ነገሮች የተጀመሩበት፣ ሀገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የዘመናዊነት እርምጃን የጀመረችበትና ነባሮቹ አስተሳሰቦች መዘመን የያዙበት አሰርት መሆኑን በርካታ የታሪክ ፀሐፊያን ይገልጻሉ፡፡ ይህም የለውጥ እንቅስቃሴ በኪነጥበቡም ላይ የራሱን ሚና ተጫውቷል፡፡

ስነ ግጥምን ስናነሳ በዚህ አሰርት ራሱን ኪነጥበብን የግጥሞቻቸው አቢይ ጭብጥ ያደረጉ የአራት ገጣሚያንን አራት ግጥሞች እናገኛለን፡፡ ቀዳሚው ግጥም የገብረ ክርስቶስ ደስታ “ከበሮ” ነው፡፡ የግጥሙ አቢይ ጭብጥ አንዱ የኪነጥበብ ዘርፍ የሆነው ሙዚቃ ነው፡፡ ከሙዚቃም የከበሮ ድምጽ፡፡ የግጥሙ ተራኪ የከበሮ ድምጽ ኃያል የሆነ ግርማ እንዳለው በመግለጽ ያገዝፈዋል፡፡ በእሱም ላይ የሚያሳድርበትን ስሜት ይነግረናል፡፡ እንዲህ እያለ፡ …ይቀሰቅሰኛል ጩኸቱን ስሰማ በሰውነቴ ላይ ይፈጥራል መሸበር ያቅበዘብዘኛል… ሌላው የዚህ አሰርት ግጥም ጥበብን ሀሳቡ ያደረገው “ሊቅና ቧልተኛ” የተባለው የመንግስቱ ለማ ግጥም ነው፡፡ ግጥሙ ገጣሚው ለኪነጥበብ ያለውን ክብር ያሳየበት ነው፡፡ የግጥሙ ማዕከላዊ ሀሳብ ጠቢብና አዋቂ መሆን እንዲሁም ለጥበብ መትጋት ነው፡፡ በዚህም መሀይም ሆኖ ከመከበርና ከመበልጸግ ይልቅ አዋቂና ጠቢብ ሆኖ መቸገርና መውደቅ እንደሚሻል ግጥሙ ያወሳል፡፡ በዚህ ዘመን የግጥሞቻቸውን አቢይ ጭብጥ ኪነጥበብ ካደረጉ ገጣሚያን መካከል ከበደ ሚካኤል በዋናነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከበደ “ለሁሉም ጊዜ አለው” በሚለው ግጥማቸው ይህንኑ ጉዳይ ጭብጥ አድርገዋል፡፡ የግጥሙ አቢይ ጉዳይ መጠየቅ ነው፡፡

ግጥሙ ታላቅ ጠቢብ የሚባለውን ሰሎሞንን ጊዜና ቦታ ሳይገታው “ሞት የሚሞትበት ግዜ መቼ ነው?” በማለት ይጠይቃል፡፡ በግጥሙ የሰው ልጅ ታላቅ “እዳ” የሆነው “ሞት” ራሱ የሚሞትበት ጊዜ ይጠየቃል፡፡ ጥያቄው የ“ነገረ ህላዌ” (የፍልስፍና) ጥያቄ ነው፡፡ የግጥሙ ሀሳብ በርካታ ፍቺዎችን ያዘምራል! እጅጉን “ተራማጅ” እንደነበረ የሚነገርለት ዮሐንስ አድማሱም ጭብጡን የግጥማቸው ጉዳይ ካደረጉ የዘመኑ ገጣሚያን አንዱ ነው፡፡ ዮሐንስ “ስንኞች” በሚል ርዕስ በጻፈው ግጥሙ በጊዜው የነበረውን ማህበረሰብ አስተሳሰብና አኗኗር ጠይቆአል፡፡ ግጥሙ ታላቅ ሀሳብን ያዘለ ጥያቄ ነው፡፡ የዘመኑ ማህበረሰብ ላይ የተሰነዘረ ጥያቄ፡፡ ግጥሙ የሚከተለውን በማለት ነው የሚቋጨው፡፡ …እራስን ረስቶ ከራስ ለማምለጡ ከራስ ለመብረር፣ ቁም ነገሩን ጥሎ፣ በከመ ፈቃድ ኑሮ እንጂ መስከር? በአሰርቱ ተገኝተው (ልብ በሉ “ተገኝተው” ነው ያልኩት) የተቃኙት እነዚህ አራት ግጥሞች ኪነጥበብን አቢይ ጭብጣቸው ያደረጉ ናቸው፡፡ ገጣሚያኑ ለጭብጦቹ የነበራቸውን አመለካከት የግጥሞቻቸው ሀሳብ በማድረግ ረገድ ተሳክቶላቸዋል፡፡

በዚህም ለኪነጥበብ ያላቸውን ክብርና ቦታ በውብ አቀራረብ አሳይተዋል፡፡ “በ1950ዎቹ ላቅ ወዳለ ኪነጥበባዊ ደረጃ የተሸጋገረው የአማርኛ ስነ ግጥም፤ በ1960ዎቹ በመጡት ገጣሚያን የመጠንና ዓይነት ለውጥ” እንዳሳየ ብርሃኑ ዘሪሁን “የአማርኛ ስነግጥም፤ አንዳንድ ነጥቦች” (2001) በተባለው ጥናታቸው ይገልጻሉ፡፡ 1960ዎቹ በሀገራችን ታላላቅ ገጣሚያን የተነሱበትና እነዚህም አዳዲስ ቅርፅንና ጭብጥን ያስተዋወቁበት ዘመን ነው፡፡ በአሰርቱ ኪነጥበብን የግጥማቸው ጭብጥ ካደረጉ ገጣሚያን መካከል ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው እና ደበበ ሰይፉ ይጠቀሳሉ፡፡ “ሙዚቃ” የተባለው የሰይፉ ግጥም ጭብጡ የኪነጥበብ ዘርፍ የሆነው ሙዚቃ ነው፡፡ ግጥሙ እጅጉን ሀሳባዊ ነው፡፡ ሙዚቃን “ሙዚቃ” ብሎ በሦስት ፊደል መግለጽ እንደማይቻል፣ ይልቁንም ሙዚቃ ከፊደልና ከቃል በላይ መሆኑን በማውሳት፣ ሊገልጹትና ሊወስኑት የማይችሉት ታላቅ ኃይል እንደሆነ ያስረግጣል፡፡ በግጥሙ “ሙዚቃ” ከልብ የሚፈልቅ ቋንቋ፣ ንግግርና እጅጉን ከፍ ያለ ሀሳብ ነው፡፡ ከፍታውም ከቃልና ከስሜት በላይ ነው! ሌላው ተወሺ ግጥም የደበበ ሰይፉ “ለአንዲት ቅጽበት ብቻ” ነው፡፡ የግጥሙ አቢይ ጉዳይ ሙዚቃና ቅኔ ናቸው፡፡ በግጥሙ የሙዚቃና ቅኔ ልዕልና ተንጸባርቆአል፡፡ ለግጥሙ ተራኪ ሙዚቃና ቅኔ ከህይወት ግሳንግስ መሸሸጊያ፣ ከማዕበል መከለያ ናቸው፡፡ “ህሊናዬን፣ ቀልቤን፣ አካሌን” ለአንዲት ቅጽበት ብሰጣችሁና ብታድሱኝ በማለት አግዝፏቸዋል፤ ከፍ ከፍም አድርጎአቸዋል! 1960ዎቹን ይወክላሉ ያልናቸውን ግጥሞች በመመልከት ለዘመኑ ገጣሚያን ኪነጥበብ እጅጉን ከፍ ያለ ክቡር ጉዳይ እንደነበር መገንዘብ እንችላለን፡፡

60ዎቹን ተሰናብተን ወደ 70ዎቹ እንቅዘፍ፡፡ እንደ ቀዳሚዎቹ አሰርት ሁሉ በ1970ዎቹም ኪነጥበብን ጭብጣቸው ያደረጉ በርካታ ግጥሞች ተጽፈዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል በከበደች ተክለአብ የተጻፈው “ጣት ወዳጁን ሲያጣ” የተሰኘው ግጥም ተጠቃሽ ነው፡፡ በግጥሙ ብዕር ታላቅ የሰው ልጅ “ፍላተ ስሜት” (ሀዘንም ቢሉ ደስታ) መተንፈሻ፣ ማቅለሚያ እንዲሁም መቀረሻ ነው፡፡ ግጥሙ ብዕርን ተናጋሪ፤ ሥፍራ የማይገታው በራሪ፤ አሮጌውን ንዶ አዲስ ስርዓትን ተካይ ነው ይለዋል፡፡ በግጥሙ ብዕር የክፉና የጭንቅ ጊዜ አወያይ፣ ቁጭትን መተንፈሻ ነው፡፡ ገጣሚዋ በሶማሊያ ወታደራዊ እስር ቤት ሆና የጻፈችው ይህ ግጥም፣ በእስር ቤቱ ያሳለፈችውን መራራ የመከራ ህይወት በብዕሯ እንዳቀለለችው ይጠቁማል፡፡ ገጣሚዋ በብዕሯ መሸበቧን አምልጣለች፤ በግጥሞቿ ለልቧ እረፍት ለስሜቷም ሀሴትን ሰጥታለች፡፡ ደበበ ሰይፉን በዚህም ዘመን ጭብጡን የግጥሙ ጉዳይ አድርጎ እናገኘዋለን- “ከያኒና ኪነት” በሚለው ግጥሙ፡፡ በግጥሙ የከያኒ እና የኪነት ምንነትና ህላዌ ተብሰልስሎአል፡፡ የግጥሙ ጭብጥ ገጣሚው በወቅቱ ይከተለው የነበረውን ርዕዮተ ዓለም የሚታገግ ይመስላል፡፡ ከያኒ ብሩህ እይታ፣ ተራማጅ አስተሳሰብ ሊኖረው እንጂ ጨለምተኛ ሊሆን እንደማይገባ ያወሳል፡፡ ከያኒው ጨለምተኛ፣ ኮናኝና ምሬተኛ ከሆነ የራሱ የከያኒውም ሆነ የኪነት ሞት እውነት እንደሚሆን ግጥሙ ይሞግታል፡፡ ለደበበ ከያኒ ብሩህ እይታ ያለውና ተስፈኛ፣ ኪነቱም ይህንኑ የሚያሳይ ብርሃንና መሪ ነው፡፡

ይህን ዘመን ተሻግረን ወደ 80ዎቹ ብናልፍም በአሰርቱ ኪነጥበብን ጭብጥ አድርገው የተጻፉ ግጥሞች (በኔ አሰሳ ልክ) አልተገኙም፡፡ በትጋት ልፈልግ ቃል ገብቼ ለዛሬው ወደ ቀጣዩ አሰርት እንለፍ፡፡ በ1990ዎቹ ኪነጥበብን የግጥሞቻቸው ጭብጥ አድርገው የጻፉ በርካታ ገጣሚያንን እናገኛለን፡፡ ከእነዚህ መካከል ነቢይ መኮንን፣ በእውቀቱ ስዩም እና ቸርነት ወልደ ገብርኤልን እናንሳ፡፡ (አላዳላሁም! ግጥሞቻቸው ጭብጡን ይወክላሉ ያልኩትን ነው የመረጥኩት፡፡) ነቢይ “ዕውነት ማነው ጅሉ” በሚለው ግጥሙ የገጣሚን ሰብዕና አግዝፎአል፡፡ ግጥሙ ጠያቂ መስሎ መላሽ ነው፡፡ የግጥሙ አቢይ ሀሳብ ገጣሚ “ጅል” እንዳልሆነ፣ “ጅል” ነው ካልንም “ጅል” ሁሉ ግን ገጣሚ እንዳልሆነ አበክሮ ይገልጻል፡፡ በዚህም ገጣሚ “ጅል” ቢመስልም ጠቢብ፣ ተላላ ቢመስልም ትሁትና ታላቅ ሰብዕና ያለው መሆኑን ይሞግታል፡፡ ከያኒው በግጥሙ ለገጣሚ ያለውን አመለካከት አንጸባርቆአል፡፡ ቀጣዮቹ የግጥሙ የመጨረሻ ስንኞች የግጥሙን ጭብጥ የሚነግሩ ናቸው፡፡ …እያንዳንዱ ጅል ግን፣ ገጣሚ እንዳልሆነ ይሄው ባንተ አየሁት፣ ባንተው ተመዘነ፡፡

የበእውቀቱ ስዩም “ሰው አለ” የተሰኘው ግጥም ሞጋች ነው፡፡ ገጣሚው በዚህ ግጥሙ የፈላስፋው የዲዮጋንን ተጠቃሽ “ሀሳብ” በሀሳብ አፍርሶአል፡፡ ማፍረሻው በአመክንዮ የተመላ ነው፡፡ ፈላስፋው ዲዮጋን “ሰው እፈልጋለሁ” ብሎ፣ በፀሐይ ብርሃን ፋኖስ ይዞ ገበያ መሀል መንከራተቱን ገጣሚው “የምን ሰው ትፈልጋለህ? ሰውን ትፈልግ ዘንድ የያዝከው ፋኖስ እኮ ሰው የሰራው ነው፡፡” በማለት የዲዮጋንን አለማስተዋል ያጋልጣል፡፡ በዚህም ትክክል ነው፤ ሃቅ ነው፤ ብለን በጅምላ የተቀበልነው ሀሳብና እውቀት ሁሉ ከጥያቄ እንደማያመልጥ አሳይቶአል፡፡ የቸርነት ወልደ ገብርኤልን “ጥበብ” የተሰኘ ግጥም አንስተን ዘመኑን እንሰናበት፡፡ ገጣሚው ጥበብ የነበረችና የምትኖር- ዘላለማዊ፤ ህያው፡፡ ስፍራ የማይወስናት “ምልዑ በኩለሄ” ነች ይለናል፡፡ በዚህም አያበቃም፡፡ ሀሳቡን ጥቅሟ ላይ በማኖር፡ …ሀይልሽን ያልተረዳ- የሁሉነትሽን የሳተ- መለኮታዊነትሽን ያልተገነዘበ፣ እሱ አበደ- እሱ ነተበ- እሱ ጠበበ በማለት የሰው ልጅ ያለ ጥበብ ከንቱና ህልውናውን ያጣ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ በዚህም የሰው ልጅ ጥበብን አጥብቆ ሊሻ፣ ሊያሳድድና ገንዘቡ ሊያደርጋት እንደሚገባ ያወሳል፡፡

እነዚህን ግጥሞች ስንመለከት፤ በአሰርቱ በጻፉ ገጣሚያን እይታ ኪነጥበብ እጅጉን ታላቅ ጉዳይ እንደነበረ መረዳት ይቻላል፡፡ ከ2001 እስከ 2006 ዓ.ም ያሉትን ስድስት ዓመታት ስንቃኝ፤ በእነዚህ ዓመታት ኪነጥበብን ጭብጣቸው ያደረጉ በርካታ ግጥሞች ተጽፈዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የሰሎሞን ሞገስን “ቋንቋ’ኮ ቁምጣ ነው” የተባለ ግጥም እናስቀድም፡፡ ግጥሙ የስነ ፅሑፍ ዋናው ጉዳይ (መገለጫ/መሳሪያ) የሆነውን የቋንቋን ቀርነት (ምልዑ ያለመሆን) ያወሳ ነው፡፡ ገጣሚው በግጥሙ ቋንቋ ሁሉን ይገልጻል፤ ሁሉን ያስረዳል፤ በማለት ቢያስብም ቋንቋን “ቀር” ሆኖ እንዳገኘው በቁጭት ይገልጻል፡፡ የግጥሙ ጭብጥ በቋንቋና ስነ ጽሑፍ ጥናት ውስጥ የሚታመነውን የመስኩን እይታ የታገገ ነው፡፡ የሰው ልጅ “ታላቅ ሀብት” የሆነው ቋንቋ፣ ምሉዕነቱ በግጥሙ ጥያቄ ወድቆበታል፡፡ የግጥሙ ገዢ ሀሳብ የቋንቋን ቀርነት ማውሳት፣ መግለጽ፣ መንገር ነው፡፡ ሌላው ግጥም የኢሰማዕከ ወርቁ “አራሚ” ነው፡፡ ግጥሙ ሀያሲን በጎ አመለካከት የሌለው፣ ከዲሲፕሊኑ የወጣና ሙያውን ያጎደፈ፤ ነቃፊና አራሚ ነው፤ በማለት ይተቸዋል፡፡ ሀያሲ ከትናንት እስከ አሁን ቢኖርም ያው፣ ያልተሻሻለና ያልተለወጠ፤ ባረም አመካኝቶ ሰብልን የሚነቅል፤ በግድፈት አመካኝቶ መልካሙን ቃልና ሀሳብ የሚነቅፍ እንደሆነ ግጥሙ ይገልጻል፡፡ የሰሎሞን ሽፈራውን “ጥበብ ፈሩን ሲስት” የተሰኘ ግጥም አንስተን ቅኝታችንን እናብቃ፡፡ የሰሎሞን ግጥም ማዕከላዊ ሀሳብ ለጥበብ መቆጨት ነው፡፡ በግጥሙ ጥበብ በዚህ ዘመን ማደፏና መጉደፏ፣ ለመልካም ነገር ከመዋሏ ይልቅ ለክፋት መዋሏ፤ ዘመኑም ጥበብ ያለው ክፋትን፣ ብልጣብልጥነትን እና መሰሪነትን መሆኑን ተወስቶአል፡፡ የግጥሙ ተራኪ ይህንን “እድፈት” በምሬት ሲተች ይስተዋላል፡፡

ይህ ዘመን በርካታ ገጣሚያን ኪነጥበብን ጭብጣቸው ያደረጉ ግጥሞችን የጻፉበት ነው፡፡ ገጣሚያኑ በግጥሞቻቸው ያንሸራሸሯቸውን ሀሳቦች ጠቅለን ስንመለከት ኪነጥበቡ “ገበያ ተኮርና ጥልቀት የለሽ” በመሆኑ የተቆጩበት ነው ማለት ይቻላል፡፡ በስድስቱም አሰርት በተጻፉ ግጥሞች ውስጥ ኪነጥበብ እጅግ ክቡር፣ ታላቅ፣ ጠቃሚ እና ገናን ጉዳይ መሆኑ ይስተዋላል፡፡ ገጣሚያኑም ለኪነጥበብ እጅጉን ቀናኢና ተቆርቋሪ ነበሩ፡፡ “ላለፉት እረፍት፤ ላሉት ህይወት ይስጥልን!” አንባቢዎቼን አንድ ነገር ላሳስብ፡፡ አስቀድሜ እንዳልኩት፣ በተጠቀሰው የዘመን ወሰን ውስጥ ኪነጥበብን ጭብጣቸው አድርገው የተጻፉ ግጥሞች እነዚህ ብቻ ናቸው የሚል እምነትም ድፍረትም የለኝም፡፡ በተለያየ ምክንያት በእጄ ያልገቡና ያልተመለከትኳቸው ግጥሞች እንደሚኖሩ እሙን ነው፡፡ ይህንን ቅኝት እየጻፍኩ ውስጤ እጅጉን የተብሰለሰለበትን ሀሳብ ሰንዝሬ ልሰናበት፡፡ ምናልባት ለቀጣይ ውይይት መነሻ ሊሆነን ይችላል፡ ኪነጥበብን ጭብጣቸው ያደረጉት አብዛኞቹ ግጥሞች (በተለይ የቅርቦቹ) ኪነጥበብ ውሉን እንደሳተ፣ ጥልቀቱን እንዳጣ፣ ከራሱ እንደተፋታ… የሚሞግቱ ናቸው፡፡ እናም ጠየቅሁ፡፡ የኪነጥበብ ውሉ ምንድን ነው? ጥልቀቱስ እስከ የት ነው? መልካም ሰንበት!!

Published in ጥበብ

እናት ልጃቸው ያለቅጥ ማምሸቱ አስግቷቸዋል፡፡ ይወጣሉ ይወርዳሉ፡፡ የ26 ዓመት ልጃቸው መጠጥ አይቀምስም፣ ብዙ ጓደኞችም የሉትም፡፡ ሁሌም በጊዜ ወደቤቱ የመግባት ዓመል ነበረው፤ዛሬ ግን የበላው ጅብ አልጮህ አለ፡፡ (የዛሬ 2 ዓመት ገደማ ነው) እናት ወገባቸውን በነጠላቸው አስረው እያቃሰቱ፣ ወደ አራዳ ክ/ከተማ ፖሊስ በመሄድ፣ ልጃቸው እንደጠፋባቸውና የሞባይል ስልኩም እንደማይሰራ እንባ በጉንጫቸው እየፈሰሰ ለፖሊስ ተናገሩ፡፡ ስሙንና መልኩንም በደንብ አብራሩ፡፡
ፖሊስ ይሄኔ የልጁ ማንነት ገባው፡፡ ወጣቱ የመኪና አደጋ ደርሶበት፣ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ድንገተኛ ክፍል ገብቶ፣ ሃኪሞች አስቸኳይ የሲቲስካን ምርመራ እንዲያደርግና ውጤቱን ፖሊሶች ይዘው እንዲመጡ አዘው ነበር፡፡ ፖሊሶችም አደጋው የደረሰበትን ወጣት፣ ወደ “ውዳሴ ዲያግኖስቲክ የምርመራ ማዕከል” በመውሰድ ምርመራው በነፃ እንዲያገኝ አደረጉ
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የአራዳ ክ/ከተማ ትራፊክ ጽ/ቤት የሥራ ኃላፊ ስለውዳሴ ዲያግኖስቲክ በሰጡት አስተያየት፤ “ምንም እንኳን ወጣቱ በደረሰበት ከባድ የመኪና አደጋ ከሞት ባይተርፍም ማዕከሉ ግን አስቸኳይ ምላሽ ሰጥቶት ነበር፤ ከእኛ ጋር በመተባበር በሚሰሩት ስራ ከፍተኛ አድናቆት አለን” ብለዋል፡፡
እንደዚህ መሰል አደጋዎች፣ አሊያም በተፈጥሮ በህመም ምክንያት በሃኪም የሲቲስካን ምርመራ ሲታዘዝ ዋጋው ከሌሎች ምርመራዎች ስለሚወደድ ብዙ ሰዎች እድሉን ሳያገኙ ለህልፈት ይዳረጋሉ፡፡ በዚህ ረገድ ያለውን የሰዎች ችግር ለመቅረፍ የሚሰራው “ውዳሴ ዲያግኖስቲክ የምርመራ ማዕከል”፤ ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ “ጳጉሜን ለጤና” በሚል መርህ፤ ከ500 በላይ ለሆኑ ሰዎች ነፃ የሲቲስካን ምርመራ እንደሚያደርግ የማዕከሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳዊት ሃይሉ አስታወቁ፡፡ ማዕከሉ በ2001 ዓ.ም ተቋቁሞ 65 ያህል ሰራተኞችን እንደሚያስተዳድር የገለፁት ስራ አስኪያጁ፤ ባለፉት ሶስት ዓመታት መርህ ከ5ሺህ በላይ ለሆኑ የሲቲስካን ምርመራ ፈላጊዎችና በራሳቸው ለመመርመር አቅም ለሌላቸው ሰዎች አገልግሎቱን እንደሰጠ አብራርተዋል፡፡
“አንድ ለትርፍ የተቋቋመ ድርጅት ከሚያገኘው ነገር ላይ አቅም የሌላቸውን መርዳትና ማህበራዊ ኃላፊነቱን መወጣት አለበት” ያሉት አቶ ዳዊት፤ በየአመቱ በጳጉሜ ወር በዘመቻ መልክ ነፃ የምርመራ አገልግሎት እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡ የማዕከሉ የማርኬቲንግ እና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወ/ሮ ሰብለ ኃይሉ እንደገለፁት፤ ከአራዳ ክ/ከተማ ትራፊክ ፅ/ቤት ጋር በመተባበር የመኪና አደጋ ደርሶባቸው የሲቲስካን ምርመራ ለሚስፈልጋቸው ሰዎች፣ በየትኛውም ሰዓትና ቀን ነፃ የምርመራ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ “ዓመቱን ሙሉ ቢያንስ ከ4-5 ሰው በየቀኑ በተለያየ ምክንያት ምርመራው አስፈልጎት ሲመጣ ነፃ ምርመራ ያገኛል” ያሉት ወ/ሮ ሰብለ፤ ጳጉሜ ላይ በዘመቻ መልክ ለብዙ ሰዎች አገልግሎቱን የምንሰጠው ሌላውም ኃላፊነቱን እንዲወጣ ምሳሌ ለመሆን ነው ብለዋል፡፡
“ምንም እንኳ ለትርፍ የተቋቋምን ብንሆንም መልካም ስራ ኪሳራ የለውም” ያሉት ወ/ሮ ሰብለ፤ ሰውን ማትረፍ መቻል በራሱ ትርፍ ነው ብለዋል፡፡ ማዕከሉ ባለፈው ዓመት ጳጉሜ ለ500 ሰዎች ነፃ ምርመራ ለማድረግ ጥሪ አቅርቦ፣ 950 ሰዎች መመዝገባቸውንና ሁሉም ነፃ ምርመራውን እንዳገኙ ተናግረዋል፡፡ የማዕከሉ ዋና ስራ አስፈፃሚ ቃለክርስቶስ ሃይሉ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫም፤ ማንኛውም የአገልግሎቱ ፈላጊ የሚመለከተው የመንግስት አካል በግሉ ለመርመር እንደማይችል ጠቅሶ ደብዳቤ ከፃፈለትና ሃኪም ምርመራው ያስፈልገዋል ብሎ ከመሰከረ፣ 500 ቢባልም የመጣው ሁሉ መመርመሩ አይቀርም ብለዋል፡፡
“ውዳሴ ዲያግኖስቲክ” በዚህ የበጎ አድራጎትና ማህበራዊ ኃላፊነትን የመወጣት እንቅስቃሴው እንደሚቀጥል የገለፁት ስራ አስኪያጁ፤ ማዕከሉ በሚገኝበት አራዳ ክ/ከተማ  ነዋሪ ለሆኑ ታካሚዎች 20 በመቶ የክፍያ ቅናሽ እንደሚደረግላቸው ተናግረዋል፡፡ ማዕከሉ ከዚህም በተጨማሪ ለክ/ከተማው ነፃ የአምቡላንስ አገልግሎት ይሰጣልም ተብሏል፡፡
ለነፃ ምርመራ ጳጉሜን ለምን መረጣችሁ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ዳዊት ሲመልሱ፤ “ጳጉሜ አሮጌው አመት አልቆ ወደ አዲስ አመት መሸጋገሪያ እንደመሆኑ መጠን፣ ሰዎች ነፃ ምርመራ አግኝተው በተስፋና በደስታ አዲሱን ዓመት እንዲቀበሉ የበኩላችንን ለማድረግ አስበን ነው” ብለዋል፡፡

Published in ዋናው ጤና

ቀይ ስጋ፣ ስብና ጨው የበዛባቸው ምግቦች አይበረታቱም  

በሳምንት ከ10 ፖርሽን (1 ፖርሽን ለአንድ ሰው የሚበቃ ምግብ መጠን ነው) በላይ ቲማቲሞችን የሚመገቡ ወንዶች በዘር ፍሬ ዕጢዎች ካንሰር (Prostate Cancer) የመያዝ አደጋን 20 በመቶ እንደሚቀንሱ በእንግሊዝ የተደረገ ጥናት ጠቆመ፡፡
የብሪስቶል ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ቡድን 20ሺህ የሚደርሱ ዕድሜያቸው ከ50-69 ዓመት የሆኑ የእንግሊዝ ወንዶችን የአመጋገብና የአኗኗር ዘዬ ያጠና ሲሆን, በየሳምንቱ ከ10 ፖርሽን በላይ ቲማቲሞችን (የተቆረጡ ቲማቲሞች፣ የቲማቲም ጭማቂ፣ በቲማቲም ሱጎ የተጋገረ ባቄላ) የተመገቡ ወንዶች በዘር ፍሬ እጢ ካንሰር የመጠቃት ዕድላቸው 18 በመቶ መቀነሱን ተመልክቷል፡፡
“የጥናት ውጤታችን ቲማቲም የዘር ፍሬ እጢ ካንሰርን በመከላከል ረገድ ጠቃሚ እንደሆነ ይጠቁማል” ያሉት ብሪስቶል ዩኒቨርሲቲ የህክምና ት/ቤት ተወካይ ቫኔላ ኢር፤ ግኝታችንን ለማረጋገጥ ተጨማሪ ጥናቶች መካሄድ አለባቸው ብለዋል፡፡
“ወንዶች በርካታ የተለየዩ ዓይነቶች አትክልቶችና ፍራፍሬዎችን መመገብ፣ ጤናማ የሰውነት ክብደታቸውን መጠበቅና አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ አለባቸው” ሲሉ መክረዋል ቫኔላ፡፡
ተመራማሪዎቹ የዘር ፍሬ እጢዎች ካንሰርን የሚከላከሉ ሌሎች ሁለት የምግብ ዓይነቶችንም መርምረዋል፡፡ ዳቦና ፓስታ በመሳሰሉት ከዱቄት የሚዘጋጁ ምግቦች ውስጥ የሚገኘው ሴሊኒየም የተባለ ንጥረ ነገር እንዲሁም ወተትና ቺዝ በመሳሰሉት የወተት ውጤቶች ውስጥ የሚገኘው ካልሲየም በፕሮስቴት ካንሰር የመጠቃት አደጋን እንደሚቀንሱ ተመራማሪዎቹ ጠቁመዋል፡፡ ቲማቲምንና ከላይ የተጠቀሱትን ሁለት የምግብ ንጥረ ነገሮች በቅጡ የሚጠቀሙ ወንዶች ለበሽታው የመጋለጥ ዕድላቸው ዝቅተኛ ነው ብለዋል አጥኚዎቹ፡፡
በጥናቱ ላይ አስተያየት የሰጡት ዶ/ር አያይን ፍሬም በፕሮስቴት ካንሰር የመያዝ አደጋን ለመቀነስ ይችሉ ዘንድ ወንዶች የትኞቹን የተወሰኑ ምግቦች መብላት እንዳለባቸው ተጨባጭ ጥቆማ ለመስጠት የሚያስችል በቂ ማስረጃ አልተገኘም ብለዋል፡፡
ወንዶች እንደ ቲማቲማ ባለ አንድ የምግብ ዓይነት ላይ ብቻ መተማመን የለባቸውም የሚሉት ዶ/ር ፍሬም፤ “ጤናማ፣ በዛ ያሉ አትክልትና ፍራፍሬዎችን ያካተተ የተመጣጠነ ምግብ ከመደበኛ የአካል እንቅስቃሴ ጋር ይበልጥ የተሻለ አማራጭ ነው” በማለት አስረድተዋል - ዶ/ር ፍሬም፡፡
የዩኬ ካንሰር ምርምር ተቋም ተወካይ ቶም ስታንስፌልድ በበኩላቸው፤ “ላይኮፒኒ በተባሉ ንጥረነገሮች የበለፀጉ እንደቲማቲም ያሉ ወይም ሴሌኒየም የያዙ ምግቦች የፕሮቴስት ካንሰር አደጋን ከመቀነስ ጋር ሊያያዙ ይችላሉ፤ ነገር ግን ይሄ ነገር አልተረጋገጠም፤ የአሁኑ ጥናት በምግብና በፕሮስቴት ካንሰር መካከል ግንኙነት ይኑር አይኑር ሊያረጋግጥ አይችልም” ብለዋል፡፡
ነገር ግን ሁሉም ወንዶች የፍራፍሬና አትክልት ይዘቱ ከፍተኛ የሆነ የተመጣጠነ ምግን እንዲያዘወትሩ እናበረታታለን ያሉት ቶም ስታንስፌልድ፤ ቀይና በፋብሪካ የተቀነባበረ ስጋ እንዲሁም ስብና ጨው የበዛባቸው ምግቦችን በእጅጉ መቀነስ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
የዘር ፍሬ እጢዎች ካንሰር በመላው ዓለም በወንዶች ላይ በስፋት የተሰራጨ ሁለተኛው የካንሰር ዓይነት ሲሆን በእንግሊዝ በየዓመቱ 10ሺ ገደማ ወንዶች በበሽታው ይሞታሉ፡፡ 

Published in ዋናው ጤና
Saturday, 30 August 2014 10:57

የጸሐፍት ጥግ

ጉድጓድ ውስጥ ስትሆን መቆፈርህን አቁም፡፡
       ዴኒስ ሂሌይ (እንግሊዛዊ የፖለቲካ መሪ)
በርቀት ያለ ውሃ በአቅራቢያ የተነሳ እሳትን አያጠፉም፡፡
ሃን ፌይ (ቻይናዊ ፈላስፋ)
ካልተሰበረ አትጠግነው፡፡
 ቤርት ላንስ (አሜሪካዊ ባለሥልጣን)
ከምናውቀው የበለጠ ብልህ ነን፡፡
ራልፍ ዋልዶ ኤመርሰን
(አሜሪካዊ ገጣሚና ወግ ፀሐፊ)
ቡትቶ ለብሰህ ተደራድረህ ሃር ልትለብስ ትችላለህ፡፡
የአይሁዶች አባባል
ታዳጊ የቀርከሃ ዛፎች በቀላሉ ይጎብጣሉ፡፡
የቬትናሞች አባባል
ጎረቤትህን እባብ ከነደፈው አንተም አደጋ ላይ ነህ፡፡
የአፍሪካዊያን (ስዋሂሊ) አባባል
እውነተኛ ወርቅ እሳት አይፈራም፡፡
የቻይናዊያን አባባል
ሚስት የሌለው ወንድ ልጓም እንደሌለው ፈረስ ነው፡፡
የቬትናሞች አባባል
ኮረዳ ወላጆቿን ለማስደሰት ስታገባ፣ ባሏ የሞተባት ራሷን ለማስደሰት ታገባለች፡፡
የቻይናዊያን አባባል
ልብ ውስጥ የተፃፈ ደብዳቤ ፊት ላይ ይነበባል፡፡
የአፍሪካዊያን (ስዋሂሊ) አባባል

Published in የግጥም ጥግ

ሜሪ ጄን ዋግል ትባላለች፡፡ አሜሪካዊት ናት፡፡ በሙያዋ የከተማ ፕላን አውጪ (Urban planner) ብትሆንም በ2013 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ መጥታ ላለፉት ሶስት ዓመታት ገደማ የስኬታማ ኢትዮጵያዊያን ሴቶችን ታሪክ የሚዘክር መፅሃፍ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ስታዘጋጅ ቆይታለች፡፡ በመጪው መስከረም ወር መጨረሻ ላይ በእንግሊዝኛና በአማርኛ ቋንቋ የተዘጋጁት የ64 ስኬታማ ሴቶችን ታሪክ የያዙ መፅሀፍት ለንባብ የሚበቁ ሲሆን መፃሕፍቱ  ታዳጊ ሴቶች ላይ አተኩረው ለሚሰሩ የስልጠና ማዕከላትና ት/ቤቶች በነፃ ይሰራጫል ተብሏል፡፡ የአዲስ አድማስ ከፍተኛ ሪፖርተር አለማየሁ አንበሴ “ተምሳፀለት  የተሰኘው መፅሃፍ ጠንሳሽና አዘጋጅ ከሆነችው ሜሪ - ጄን ዋግል ጋር በመፅሃፉ ዙሪያ ያደረገው ቃለምልልስ እንዲህ ቀርቧል፡፡

          የስኬታማ ኢትዮጵያዊያን ሴቶችን አጭር የህይወት ታሪክ የሚዘግብ መፅሀፍ ማዘጋጀትሽን ሰምቻለሁ፡፡ መፅሃፉን ለማዘጋጀት ምን አነሳሳሽ? እስቲ ስለመፅሃፉ ጠቅለል አድርገሽ ንገሪኝ…
ወደ ኢትዮጵያ የመጣሁት እ.ኤ.አ በ2011 ዓ.ም ነው፡፡ አመጣጤም ከትውልድ ሃገሬ ውጪ ያሉኝን ልምዶች ለማካበት ነበር፡፡ በአጋጣሚ የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ጥምረት ፕሬዚዳንት ከሆኑት ወ/ሮ ሳባ ገ/መድህን ጋር የሃገሪቱ ሴቶች ላይ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተፃፉ መፅሃፎችን ማፈላለግ ጀመርኩ፡፡ ነገር ግን እንዳሰብኩት ላገኝ አልቻልኩም፡፡ በወ/ሮ መአዛ አሸናፊ የተፃፈው የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎን የሚተርክ መፅሃፍ ብቻ ነው ላገኝ የቻልኩት፡፡ ከዚህ ቀደም በሌሎች የአፍሪካ ሃገሮች በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተፃፉ የታላላቅ ሴቶችን ታሪክ አግኝቻለሁ፡፡ የኢትዮጵያዊያንን ስኬታማ ሴቶች የሚዘክር መፅሃፍ ግን ላገኝ አልቻልኩም፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተደራጀ መፅሃፍ ማዘጋጀት ቢቻል፣ የሃገሪቱ ታዳጊ ወጣት ሴቶች የቀደሙትን ሴቶች ታሪክና ልምድ እንዲሁም ጥንካሬ በሚገባ ተረድተው እንዲያድጉ ማድረግ ይቻላል በሚል መፅሃፉን ለማዘጋጀት ወሰንኩ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ወ/ሮ ሳባን ሳማክራት በጣም ተደሰተች፡፡ መፅሃፉ ጠቃሚ ነው ቀጥይበት አለችኝ፡፡
በዚህ መልኩ ስለውጤታማ ሴቶች መረጃዎች ማሰባሰብ ጀመርኩ፡፡ አብዛኞቹ ታሪኮች በጋዜጣና በመፅሄቶች ተበታትነው የሚገኙ ከመሆናቸውም በላይ ያልተሟሉ ናቸው፡፡ የተወሰኑ የአዲስ አበባ የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን መርጠን መረጃዎችን በመፈለግ እንዲረዱን ጠየቅን፡፡ እነሱም ትብብራቸውን አልነፈጉንም፡፡ የታሪኩ ባለቤቶችና ቤተሰቦቻቸውን አፈላልጎ በማግኘት፣ ቃለመጠይቆችን ማድረግ፣ በእነሱ ዙሪያ የተፃፉትን ዘገባዎች ማሰባሰብና ሌሎችንም የስራው ሂደቶች አብረን ተወጥተናል፡፡ ሁሉም ሲያገለግሉ የነበረው በበጎ ፈቃደኝነት ነበር፡፡
በዝግጅቱ ወቅት ቃለመጠይቅ የተደረገላቸው ባለታሪኮች ራሳቸው ቃለ መጠይቃቸውን በራሳቸው ቋንቋ አርመው እንዲመልሱልን አድርገናል፡፡ ከ300 በላይ ሴቶች ነበሩ የተመረጡት፤  ከዚያ ውስጥ ነው ወደ 64 የሚሆኑት ተመርጠው በመፅሃፉ የተካተቱት፤ ነገር ግን የሁሉም ታሪክ ለታዳጊ ሴቶች የሚያጋራው የራሱ ነገር አለው፡፡ ለዚህ ሲባል በድረገፃችን ላይ የሁሉንም ሴቶች ታሪክ አስፍረናል፡፡
ፎቶግራፎችን በተመለከተም ታዋቂዋ ፎቶግራፍ አይዳ ሙሉነህ እንድታነሳ አድርገናል፡፡ ለሁለት አመት ገደማ የእነዚህን ባለታሪኮች ፎቶግራፍ ስታሰባስብና በስራ ላይ እያሉ ስታነሳ ቆይታለች፡፡ ፎቶግራፎቹ አለማቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁና ጥራት ያላቸው ናቸው፡፡ የታተመውም በአሜሪካን ሃገር ሎሳንጀለስ በሚገኘው ፀሃይ ፕሬስ ማተሚያ ቤት ነው፡፡
በመፅሃፉ የተካተቱት ባለታሪኮች እንዴት ነው የተመረጡት?
በመፅሃፉ የተካተቱ ባለታሪኮችን ስንመርጥ ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርገናል፡፡ ሴቶቹ ከተለያዩ የስራ ዘርፎች የተመረጡ ናቸው፡፡ ገበሬ ከሆኑት ጀምሮ የህዝብ መሪ እስከሆኑት ሴቶች ድረስ በጥልቀት ለመዳሰስ ተሞክሯል፡፡ የመጀመሪያዋ አውሮፕላን አብራሪ ሴት፣ የኮንስትራክሽን ክሬን ባለሙያ፣ አርቲስት፣ ሃኪም አምባሳደር… የመሳሰሉት በመፅሀፉ ተካተዋል፡፡ ከተለያዩ የሙያ ዘርፎች ለመምረጥ ተችሏል፣ ከኪነ- ጥበብ፣ ከማህበራዊ እንቅስቃሴዎች፣ ከህዝብና የመንግስት ሰራተኞች፣ ከመገናኛ ብዙሃን፣ በቢዝነስ ስኬታማ ከሆኑት፣ ከህክምና ሌሎችም የተመረጡ ናቸው፡፡ ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ እንዲሆኑም ጥረት ተደርጓል፡፡ 64 ሴቶችን ብቻ ስንመርጥ በሃገሪቱ ስኬታማ እነዚህ ብቻ ናቸው ማለታችን አይደለም፡፡ የግዴታ መምረጥ ስላለብንና ማሳያ ይሆናሉ ብለን ስላሰብን እንጂ፡፡ የ300ዎቹን ሴቶች ታሪክ በሙሉ በመፅሃፉ ባናካትትም ድረገፃችን ላይ ታሪካቸው እንዲቀመጥ አድርገናል፡፡ ለወደፊት ታሪካቸው  በሌላ መፅሃፍ ታትሞ ሊወጣ ይችል ይሆናል፡፡ የ64 ሴቶች ታሪክ የያዘው ይህ አዲስ መፅሀፍ ግን የአዲስ ዓመት ስጦታ ይሆናል፡፡
የመፅሃፉ ፋይዳ ምንድን ነው? የትኛውን የህብረተሰብ ክፍልስ ያለመ ነው?
መጀመሪያ መፅሀፉ ታሳቢ የሚያደርገው ታዳጊ ሴቶችን ነው፡፡ እነዚህ ታዳጊዎች ለወደፊት የህይወት አቅጣጫቸውን ለመወሰንና በጥንካሬ ለመጓዝ ባለታሪኮቹ ምሳሌ ይሆኗቸዋል፡፡ ብዙውን ጊዜ የሚታሰበው ሴቶች ትምህርት ተማሩም አልተማሩም የሆነ እድሜ ላይ ሲደርሱ ባል ማግባት እንዳለባቸው ብቻ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ወይ የቤት እመቤት ይሆናሉ አሊያም ባሎቻቸውን በስራ የማገዝ ኃላፊነት ይሸከማሉ፡፡ ትልቅ ደረጃ ስለመድረስ አይታሰባቸውም፡፡ ነገር ግን የእነዚህ ሴቶች የህይወት ተሞክሮ ስኬታማ መሆን እንደሚቻል ለታዳጊዎች በሚገባ ያስተምራል፡፡ ማድረግ የሚፈልጉትን ለማድረግ ምንም የሚሳናቸው ነገር እንደሌለ የባለታሪኮቹ ታሪክ ለታዳጊዎቹ ያሳያል፡፡
በመፅሀፉ ዝግጅት ወቅት ፈታኝ የነበሩ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?
አንዱ ትልቁ ፈተና የነበረው ሴቶቹን ማግኘት ነው፡፡ አንዳንዶቹ ታሪካቸውን ለመናገር አይደፍሩም፤ እንደውም የአንዷን ሴት ታሪክ ለማግኘት 3 ጊዜ ያህል መመላለስ ግድ ሆኖብን ነበር፡፡ የኢንተርኔት፣ የስልክ ችግሮችም ነበሩ፡፡ ሴቶቹን እንደልብ ማግኘት አንችልም ነበር፡፡ ታሪኮቹን ማረምም የራሱን ሰፊ ጊዜ ወስዷል፡፡ በመፅሃፉ ዝግጅት ላይ የተሳተፉትን ሰዎች ጊዜ ከተገቢው በላይ የተሻማ መፅሀፍ ነው፡፡ የተሰባሰቡትን መረጃዎች በፅሁፍ፣ በፎቶግራፍ፣ በዲዛይን ማቀናበር በራሱ አስቸጋሪና ጊዜ የወሰደ ነበር፡፡ ነገር ግን በበጎ ፈቃደኝነት የተሳተፉ ተማሪዎችን ጨምሮ የፎቶግራፍ እና ዲዛይን ስራውን የከወኑት ባለሙያዎች ለስራቸው ታማኝ በመሆናቸው ውጤታማ መሆን ተችሏል፡፡
መፅሃፉን ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ  መተርጎም በራሱ ከባድ ነበር፡፡ የትርጉም ስራውን የሰራው ኢዮብ ካሣ እና የፊደል ለቀማ (Proof readeing) የሰሩት ሰዎች እጅግ የሚደንቅ ስራ ሰርተዋል፡፡ ከእነዚህ ሰዎች ጋር በመስራቴ ኩራት ይሰማኛል፡፡
የገንዘብ ድጋፍ ያደረገው ማን ነው?
በአብዛኛው የመፅሃፉ ዝግጅት የተሰራው በበጎ ፍቃደኞች እገዛ ነው፡፡ መፅሃፉ ለንባብ ሲበቃ ለሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች፣ ለቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛዎችና ለመሳሰሉት የትምህርት ተቋማት በነጻ ነው የሚሰራጨው፡፡ በመፅሃፉ ዝግጅት ወቅት 13 ያህል ተቋማት ትብብር አድርገውልናል፤ ድጋፋቸውንም ቸረውናል፡፡ የስዊድን መንግስት፣ ኮካኮላ ኩባንያ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሴቶች ጉዳይ፣ የእንግሊዝ አለማቀፍ የልማት ተቋም (DFIO)፣ የአውሮፓ ህብረት፣ የፈረንሳይ ኤምባሲ፣ የአሜሪካ ኤምባሲ፣ አይፓስ ኢትዮጵያ፣ ዴቪዲና ሉሲ አለማቀፍ ፋውንዴሽን፣ ፓዌ ኢትዮጵያ፣ አይርሽ ኤይድ የተለያዩ ድጋፎችን አድርገውልናል፡፡ መፅሀፉ ታዳጊ ሴቶችን በተለያዩ ሙያዎች ለሚያሰለጥኑ የትምህርት ተቋማት በነፃ እንዲበረከት የእነዚህ ተቋማት ድጋፍ ወሳኝ ሚና አለው፡፡
መፅሀፉ መቼ ነው አንባቢያን እጅ የሚደርሰው?
የመጀመሪያው የመፅሃፉ ህትመት ለሽያጭ አይቀርብም፡፡ እንዳልኩህ በነፃ ነው የሚታደለው፡፡ በቀጣይ የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ጥምረት የእንግሊዝኛና የአማርኛ ትርጉም መፅሃፉን ይፋ ሲያደርግ ምናልባት ለሽያጭ ሊቀርብ ይችላል፡፡ የዚህ መፅሃፍ ምረቃ የሚካሄደው መስከረም 27 ቀን 2007 ዓ.ም ነው፡፡ የምረቃ ቦታውም በብሄራዊ ሙዚየም ይሆናል፡፡ የፎቶግራፍ ባለሙያዋ አይዳ ሙሉነህ ያነሳቻቸው ፎቶዎችም በኤግዚቢሽን መልክ ይቀርባሉ፡፡ በሌሎች ሃገሮች ተመሳሳይ ፕሮጀክቶች ላይ ሰርተሽ ታውቂያለሽ?
አይ! በሌላ ሃገር እንዲህ አይነት ስራ ላይ ተሳትፌ አላውቅም፡፡ በሙያዬ የከተማ ፕላን አውጭ ነኝ፡፡ በአሜሪካ በቤቶች ልማት ላይ  ሰርቻለሁ፡፡ በመፅሃፍ ዝግጅት ደረጃ የአሁኑ የመጀመሪያዬ ነው፡፡
በኢትዮጵያ የነበረሽን ቆይታ እንዴት ትገልጭዋለሽ?
ኢትዮጵያን በጣም ወድጃታለሁ፡፡ አስደናቂና ውብ ሃገር ነች፡፡ ባህሉ ጥልቅ ነው፣ በቤተሰብና በሃይማኖት ዙሪያ ማዕከል ያደረገ ትስስሮሽና ባህል አላችሁ፡፡ ሰው አሜሪካ በበጎ ፍቃደኝነት አገልግሎት የተሻለች ናት ሲል እሰማለሁ፤ እኔ ግን እዚህም የበጎ ፍቃደኝነት አገልግሎት ለመስጠት ከፍተኛ ቁርጠኝነት እንዳለ በሚገባ አይቻለሁ፡፡ የሃገሬውን ምግቦችም ወድጃቸዋለሁ፤ ሽሮ ወጥ በጣም ነው የምወደው፡፡ ማኪያቶው ደግሞ የትም ሃገር የማይገኝ ልዩ ጣዕም ያለው ነው፡፡
ቀጣይ እቅድሽ ምንድን ነው?
መፅሀፉ ከተመረቀ በኋላ ወደ አሜሪካ እመለሳለሁ፡፡ መኖሪያ ቤቴ ሎስ አንጀለስ ነው፡፡ በሎስ አንጀለስ መደበኛ ስራዬን እቀጥላለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ በኢትዮጵያ የሰራሁትን ፕሮጀክት እዚያም ለመስራት እቅድ አለኝ፡፡
ስለቤተሰብሽ ሁኔታ ልትነግሪኝ ትችያለሽ?
አግብቼ ሶስት ልጆች ወልጄ ፈትቻለሁ፡፡ ሶስት ቆንጆ ሴት ልጆች አሉኝ፡፡ ሁሉም በተለያየ ቦታ ነው የሚኖሩት፡፡ አንዷ ህንድ፣ ሌላዋ ሎስአንጀለስ፣ አንዷ ደግሞ ኒውዮርክ ነው የምትኖረው፡፡ አያትም ሆኛለሁ፤ በህንድ ሁለት የልጅ ልጆች አሉኝ፡፡ ለ5 ዓመት በህንድ ኖሬያለሁ፣ ይሄ ደግሞ የተለያዩ ባህሎችን ለማወቅ አግዞኛል፡፡ ወደ ትምህርት ሁኔታ ስመጣ በከተማ ፕላን ሁለተኛ ዲግሪ አለኝ፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪ በመንግስት አስተዳደር ወስጃለሁ፡፡  በተማርኩባቸው የሙያ መስኮች በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎችም ሃገሬን አገልግያለሁ፤ በማገልገል ላይም እገኛለሁ፡፡

Published in ህብረተሰብ

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…የዚህ ዓመት ‘ፍጥነት’ አይገርማችሁም! እንኳንም ተንደረደረ! ልክ ነዋ… ደስ የማይሉ  ነገሮች ‘ሚዛን የደፋበት’ ዓመት ነዋ! ‘ጦስ ጥምቡሳሳችንን’ ይዞ ይሂድማ!
ነገርዬው ምን መሰላችሁ… የሚያሳዝነው ደግሞ ለከርሞም ደመናው ስለመገለጡ እርግጠኛ ሆነን መናገር አለመቻላችን ነው፡፡ መሽቀንጠር ያለባቸው ትከሻችን ላይ የተከመሩ ችግሮች በዙብና!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ‘ባቡሩ’ ለከርሞ ሲመጣ እኛን “ጥርግርግር አድርጎ…” መውሰዱ ‘እንደተጠበቀ ሆኖ’ መጪው ዓመት የከፉ ነገሮቻችንን ጠራርጎ ሚሲሲፒ ወንዝ የሚከትልን ዓመት ይሁንልን ብለን እንመኝ! አሜን!
ታዲያላችሁ… ዙሪያችንን የከበበን የጥላቻ ጥልፍልፎሽ ይቺን አገር የት ሊያደርሳት ነው አያስብላችሁም! ኮሚኩ ነገር ምን መሰላችሁ…ዘንድሮ ለመጠላላት ምንም ‘ርስት መግፋት’ ‘ሚስት መንጠቅ’ ምናምን አያስፈልግም፡፡
እናማ…በማንነታችን፣በትውልድ ስፍራችን፣ በእነከሌ ዘመድነታችን…ምናምን በቀላሉ የምንጠላላበት ዘመን ነው፡፡ ሁሌ ሽክ በማለታችን፣ የደላን በመምሰላችን…ምናምን የምንጠላላበት ዘመን ነው፡፡ ‘ሳያልፍልን’ በመኖራችን፣ ሰባራ ሳንቲም የሌለን ‘መናጢ’ ድሆች በመሆናችን፣ ዕድል ፊቷን ያዞረችብን በመሆናችን…ምናምን የምንጠላላበት ዘመን ነው፡፡ታዲያላችሁ…ቀሺሙ ነገር ምን መሰላችሁ… ይህ የመጠላላት ‘የድንጋይ ዘመን’ ባህሪይ ወደ ትኩሱ ትውልድም መጋባቱ! በየስፖርቱ፣ በየሙዚቃው፣ በየትወናው… ምናምን ያለው የእርስ በእርስ መጠላላት የሚገርም ነው፡፡ እነኚህንና የመሳሰሉ ዘርፎችን የሞሉት የነገው ‘አገር ተረካቢ ትውልድ’ አባላት ናቸው፡፡ እናማ… መጪው ዓመት ጥላቻን “ጥርግርግ” አድርጎ ይወሰድልንማ!
ደግሞላችሁ…መናናቅ ይችን አገር የት ያደርሳት ይሆን የምንልበት ዘመን ላይ ነን፡፡ ለመናናቅም ቢሆን መስፈርቶቹ የግል ቁርሾ ምናምን አይደሉም፡፡ ወይም ገሚሶቻችን ‘ተባርከን’ ገሚሶቻችን ደግሞ ‘ተረግመን’ ወደዚች ዓለም ስለመጣን አይደለም፡፡ ወይም…አለ አይደል… “ተንቀህ ኖረህ ተንቀህ ይቺን ዓለም ተሰናበት…” ምናምን የሚል ግዝት ስላለብን አይደለም፡፡
የኢኮኖሚ አቋማችን ‘ከወለሉ በታች’ ስለሆነ ብቻ ‘እንናቃለን’፣ በምርጦች መሰባሰቢያ የቀለጡ መንደሮች አካባቢ ስለማንታይ ‘እንናቃለን’፣ የመጣንበት የዘር ግንድ ‘እንናቃለን’፣ በ‘ቦተሊካው’ በሚኖረን አመለካከት ‘እንናቃለን’፣ ሰዉ ሁሉ በየግል መኪናው ሲንፈላሰስ እኛ በዘጠኝና አሥራ አራት ቁጥር አውቶበሶች ተጠቅጥቀን ከቦታ ቦታ በመሄዳችን ‘እንናቃለን’፣ እንትናዬአችን ጸጉሯን የምትተኮሰው በየመንፈቁ በመሆኑ (ቂ…ቂ…ቂ…) ‘እንናቃለን’ በፈረንጅ አፍ “ሀው ኢዝ ዩ?”   “ኮንፊደንሻል ነኝ” ምናምን ማለት ባለመቻላችን ‘እንናቃለን’፡፡
እናላችሁ…መጪው ዓመት የመናናቅ ቫይረስን ጠራርጎ ይሂድልንማ!
እግረ መንገዴን ይቺን ስሙኝማ…ሁለት የናጠጡ ሀብታሞች ይፎካከራሉ አሉ፡፡ እናላችሁ…አንደኛው ምን ይላል… “እኔ ሚሊየነር ነኝ፡፡ አንተን ገዝቼ ልሸጥህ እችላለሁ፣” ይላል፡፡ ሁለተኛው ምን አለ መሰላችሁ…“እኔ ቢሊየነር ነኝ፡፡ አንተን ገዝቼ አስሬ አስቀምጥሀለሁ፡፡ መሸጥ አያስፈልገኝም!”
እናላችሁ…“አንተን ገዝቼ ውሻ ቤት አስሬ አስቀምጥሀለሁ…” ማለት የሚቃጣቸው ሰዎቸ እየበዙ ሲሄዱ ጥሩ ምልክት አይደለም፡፡  
ደግሞላችሁ…በሆነ ባልሆነው እርስ በእርስ መጠራጠር “ይቺን አገር የት ያደርሳት ይሆን!” የምንልበት ዘመን ላይ ነን፡፡ እናማ…አንዳችን ሌላኛችንን ለመጠርጠር ምንም ምክንያት አያስፈልገንም፡፡ እንዲህም ሆኖ እርስ በእርስ እንድንጠራጠር የሚያደርጉን ነገሮች አንድ መቶ አንድ ናቸው፡፡
መዝናኛ ስፍራ ላይ ሰዉ ሲያውካካ ብቻችንን ጥግ ይዘን በመቀመጣችን ‘እንጠረጠራለን’፣ እንደ ሌላው ሁሉ የትውልድ ቀዬአችን እዚህ ወይም እዛ ስፍራ በመሆኑ ‘እንጠረጠራለን’፣ አብረን ሻይና ጃምቦ ድራፍት በምንጠጣቸው ሰዎች ማንነት ‘እንጠረጠራለን’፣ በምናነባቸው የህትመት ውጤቶችና በምንከታተላቸው መገናኛ ብዙሀን ምንነት ‘እንጠረጠራለን’፣ ሌላው ከ‘ቅንጭላቱ’ አንድ ሁለት ብሎን በፈቃደኝነት አስወግዶ ‘ጨርቁን ሲጥል’ እኛ ግን “በገዛ እጄማ ጨርቄን አልጥልም…” በማለታችን ‘እንጠረጠራለን’፣ በምናደንቃቸው ወይም በማይመቹን ደራስያን፣ ገጣሚዎች፣ ተዋናዮች ምናምን ማንነት ‘እንጠረጠራለን’፣ የምናጨበጭብላቸው ‘ቦተሊከኞች’ (አሉ እንዴ!) እዚህ ወይም እዛኛው ቡድን ውስጥ በመሆናቸው ‘እንጠረጠራለን’፡፡  
እናላችሁ…ዘንድሮ አይደለም ባስ ያሉ ጉዳዮችን፣ የግል ጉዳዮችን ስናወራ እንኳን አንዳችን ሌላኛችንን በሆዳችን…አለ አይደል… “ሂድና የግሪክ ቱሪስት ብላ!” ምናምን እንባባላለን፡፡ ምን መሰላችሁ…የሚነገሩ የተለመዱ አባባሎች እንደየሰዉ  እየተከተፉና እየተከታታፉ “ጤና ይስጥልኝ!” ለመባባል እንኳን  አይመችም፡፡ ታዲያላችሁ…“ምን አግኝተህ ነው እንዲሀ ያማረብህ!” አይነት አባባል በፊት የወዳጅነት ጨዋታ ነበር፡፡ ተናጋሪም ሆነ አድማጭ ‘ተቀጥላ’ ትርጉም አይፈልጉለትም ነበር፡፡
ዘንድሮ ግን ታሪኩ ተለውጧል፡፡ “ምን አግኝተህ ነው ያማረብህ?” አይነት አባባል… መአት ነገር ሆኖ ሊመነዘር ይችላል፡፡ እናማ… እናንተ በወዳጅነት መንፈስ “ምን አግኝተህ ነው ያማረብህ?” ስትሉ…
“ስኳር ልሰሀል ወይ ማለቱ ነው እንዴ?”
“በእሱ ቤት እኮ ከሰዎቹ ተጠጋህ ማለቱ ነው፡፡”
“እንግዲህ ያቺን የሆቴል ቤት ባለቤት ስለያዝኩ ገንዘብ አይቶ ገባ ሊል ነው፡፡”
“ሰው የማያውቀው የድብቅ ገቢ አለህ ሊል ፈልጎ ነው እንዴ!” ምናምን እየተባለ አንድ መቶ አንድ ሰበብ ሊሰጥ ይችላል፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ሁለትም ሦስትም ሆነው እየተዝናኑ ሳለ የተከፈተ ለስላሳ ወይም ቢራ ትቶ ወደ መጸዳጃ መሄድ እየቀረ ነው ይባላል፡፡ አሳላፊ ተስተናጋጁ አጠገብ ደርሶ እየታየ መጠጡን ካልከፈተው በስተቀር ከፍቶ ያመጣውን መጠጥ መጠጣት እየቀረ ነው አሉ፡፡ ምግብ ተመግበው ዘወር ካሉ በኋላ ተመልሶ መጥቶ መጉረስ እየቀረ ነው አሉ፡፡
 እናላችሁ…እርስ በእርስ የመጠራጠራችን ነገር አየደለም በ‘ሲኒየር ሲቲዘንስ’ አካባቢ…አለ አይደል… በወጣት የኪነጥበብና የስነ ጥበብ ሰዎች ዘንድ ሁሉ እየተስፋፋ ነው ይባላል፡፡ እናላችሁ…የምናየው ነገር ሁሉን “ይቺን አገር የት ያደርሳት ይሆን!” የሚያሰኙ እየሆኑ ተቸግረናል፡፡
መጪው ዓመት እርስ በእርሳችን በሆነ ባልሆነው የማንጠራጠርበት ዓመት ይሁንልንማ!
ታዲያላችሁ…“ኑሮ እንዴት ነው?” ምናምን ስንባል “አሸወይና ነው…” ምናምን አይነት አስተያየት የምንሰጥበትን ጊዜ ያቅርብልንማ!
እናማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ፣ የአስተያየት ነገር ካነሳን አይቀር፣ ይቺን ስሙኝማ……አንዳንድ ‘ፈረንጅ’ ጎብኚ አስተያየት ሲሰጥ ልብ ብላችሁልኛል! ታዲያላችሁ…አገሪቱን እንደሚወድ ምናምን ይናገርና… “ለመሆኑ ስለ አገራችን የምታደንቀው ምንድነው?” ሲባል ምን ይላል መሰላችሁ… “ሴቶቻችሁ ቆንጆዎች ናቸው…” ብሎላችሁ እርፍ!
እኔ የምለው…‘ፈረንጅ’ እዚህ አገር ሲመጣ በአእምሮው ማሰቡን ትቶ ለሌላ አገልግሎት በተመደበለት (ቂ...ቂ…ቂ…) የሰውነት አካል ነው እንዴ የሚያስበው!
ይቺን ስሙኝማ…
አሰማራቸውና ከብቶቻችን ይብሉ፣
አሰማራቸውና በጎቻችን ይብሉ፣
አሰማራቸውና ከብቶቻችን ይብሉ፣
ያ ሣር አይደለም ወይ የምናየው ሁሉ፣
የሚሏት የጥንት አባባል አለች፡፡ መጪውን ዓመት የአሣር ከመሆን አንድዬ ይጠብቅልንማ!
እናማ…“…ይቺን አገር የት ያደርሳት ይሆን!” የሚያስብሉ ነገሮች የሚቀንሱበት ዓመት ይሁንልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!



Published in ባህል

           ከተማዋ “ፋጥግዚ” ነበር የምትባለው፡፡ አንበሳና ነብር የሚውልባት ዱር ጫካ ነበረች፡፡ እጅግም ታስፈራ ነበር፡፡ ልጆች ሳለን ከብት አግደን፣ አደን አድነን፣ ገበሬዎች ሆነን አድገንባታል፡፡
አሁን ግን ከተራራ እና ድንጋይ በቀር ጫካና ሸለቆ አላየሁም
ጥንት እኮ ነው የምልሽ..አሁንማ መሬቱም አረጀ መሰለኝ.. ድንጋዩም ቆላውም በረታ፡፡ በጦርነትና በድርቅ  እጅግ ተጎድቷል፡፡ ኢትዮጵያን ካቀኑዋት ሶስቱ ቀደምት ህዝቦች መካከል አንዷ ሰቆጣ ስትሆን ሌሎቹ አክሱምና ጎንደር ናቸው፡፡ ባህላችን፣ ታሪካዊ ቅርሶቻችንና ቋንቋችን የከተማዋን ጥንታዊነት ያሳያሉ፡፡
ያኔ ሰዎች ከስፍራ ስፍራ ሲንቀሳቀሱ በዘራፊዎች ንብረታቸውን ይቀሙ ስለነበረ፣ ገንዘባቸውንና  ወርቃቸውን ዙሪያ ገቡን በምታይው ተራራና ድንጋያማ ስፍራ ይደብቁ ወይንም ይሸጉጡ ነበር፡፡ ሰቆጣ የሚለው የመጣው “ገንዘቡን ሸሸገ..ሸጎጠ..ሰቆጠ..” ከሚለው ሲሆን ከተማዋም “ሰቆጣ” ተባለች፡፡
የዋግኽምራ ዋና ከተማ ከሆነችው ሰቆጣ በ5 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውንና በአጼ ካሌብ ዘመነ መንግስት ከአንድ አለት ተፈልፍሎ የተሰራውን የላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያን በአምስት መቶ ዓመት የሚበልጠው ውቅር መስቀለ ክርስቶስ፤ የስፍራውን ጥንታዊነት ያሳያል፡፡ በህንጻው ጣሪያ ላይ የላቲንና የግሪክ የሚመስሉ ጥንታዊነት ያላቸው መስቀሎች ሲኖሩት የእብራይስጥ ቋንቋ ጽሑፎችም አሉት፡፡ ከህንጻው ስር መሬት ለመሬት እስከ ውቅር ላሊበላ ድረስ የሚወስድ መንገድ አለው፡፡ (ውቅር መስቀለ ክርስቶስን በጎበኘሁበት ወቅት የደብሩ አለቃ፤ በአንድ ወቅት አንድ የውጭ አገር ዜጋ ኦክስጅንና መብራት ይዞ በውስጥ ለውስጥ ዋሻው ለ20 ደቂቃ ከተጓዘ በኋላ አየር አጠረኝ ብሎ መመለሱን የነገሩኝ ሲሆን ዋሻው ከሰቆጣ ከተማ 128 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኘው የላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት ጋር  እንደሚያገናኝ ገልፀውልኛል፡፡)፡፡ በቤተክርስቲያኑ ውስጥ የዋግ ሹሞች ቅሪተ አካላት ይገኛሉ፡፡
በህገ ኦሪት (ከክርስቶስ ልደት በፊት) ጊዜ እንደተሰሩ የሚነገርላቸው የሰላምጌ ማሪያም፤ የደብረ ጸሐይ ወይብላ ማርያምና የመሳሰሉት አድባራት በዚሁ አካባቢ ነው የሚገኙት፡፡ ህዝብና አካባቡው አሁን ላለው መንግስት (ኢህአዴግ) ባለውለታ ናቸው ይባላል..
ደርግን ለመንቀል እንቅስቃሴ ሲደረግ አሮጌው፣ ቆንጆው፣ ውርጋጡ…  በዓል ነው፣ አዘቦት ነው ሳይል ወፍጮ ፈጭቶ፣ ጋግሮ፤ ስንቅ ቋጥሮ፣ ከዱር ያሉ ልጆች እንዳይርባቸው እንዳይጠማቸው አድርጎ ነው ለዛሬ ወግ ማዕረግ ያበቃቸው፡፡ አይደለም ህዝቡ የአካባቢው ተፈጥሮም ለእነሱ ባለውለታ ነው፡፡ ልጄዋ! ይሄ አካባቢማ “ራበኝ፣ ጠማኝ” ሳይል ነው የኖረ፡፡
 ደሞስ ካልሽስ… ከእኛ የወጡ አይደሉ ታጋዮችስ ብትይ፡፡ ጨቃኙ ደርግ እነሱን “ሸሽጋችኋል” ብሎ አስራ አንድ ጊዜ በጀት ደብድቦናል፡፡ ቀን በዱር ውሎ፣ ማታ  ወደ ከተማ መጥቶ፣ ለሊት ገበያ ወጥቶ… የዛሬዎችን አመራሮች አሳድጎበታል፡፡
እርስዎ ያኔ ምን ይሰሩ ነበር?
የደርግ ታጣቂ ሆኜ ሳገለግል ወያኔዎቹ ይዘው አስረውኝ ነበር፡፡ በጫካ በእስር ላይ ሳለሁ ልብስ ሰፊ ነበርኩ፤ ክላሽ መያዣ ሳይቀር ትጥቃቸውን እኔ ነበርኩ የምሰፋላቸው፡፡
ለተወሰነ ጊዜ አብሬያቸው እየተዟወርኩም፣ የትጥቅ ልብሳቸውን እሰፋ ነበር፡፡ በኋላ ሌሎችንም ልብስ መስፋት አስተምሬአቸዋለሁ፡፡
እስቲ የእነማንን ልብስ ሰፍተዋል?
ውው… የብዙዎቹን የብአዴን ልጆች የትጥቅ ልብስ እኔ ነበርኩ መትሬ የምሰፋላቸው፡፡ በስም ያልሽኝ እንደሁ አላስታውሳቸውም፡፡ ግን እጅግ ጥሩ አድርጌ ነበር የምሰፋላቸው፡፡ ሁለት ሌሎች ልብስ ለመስፋት ፍላጎት ያላቸውን ልጆች አሰልጥኜ የእኔን ስራ ይሰሩ ነበር፡፡  ያን ጊዜ የነበራቸውን ቁርጠኝነትና ጀግንነት ሳስበው ይደንቀኛል፡፡ ወንዱ ገበሬ መስሎ፣ ሴቲቱ እንቁላል የምትሸጥ አልባሌ ሆና ትመጣለች፡፡ የገበሬ ሚስት ወይም ልጅ ትሆናለች ብለን እናስባለን፡፡ አብረውን ይበሉ፣ ይጠጡ ነበር፡፡ ገብተው ምን ሰርተው እንደሚወጡ እንኳን አይታወቁም፡፡ ውስጥ ለውስጥ የልባቸውን ይሰራሉ… መቼም ጀግናዎች ናቸው፤ ብለው ብለው ደርግን ነቅለው ጣሉት፡፡
በደርግ ዘመን ሰቆጣን መንግስት አያስተዳድራትም ነበር ሲባል ሰምቻለሁ…
አዎ፡፡ እንደውም እነዚህም ሳይገቡ ደርግ መንግስት ሆኖ እየመራ፣ ከተማዋን ሌባ ገብቶ እንዳይሰርቃት፣ እኔን ጨምሮ አስራ ሁለት ሰዎች ተመርጠን እንጠብቃት ነበር፡፡ በወቅቱ እኔ ሰብሳቢ ነበርኩ፡፡ የሰቆጣ ህዝብ ደርግ በቀይ ሽብር ሁለትና ሶስት ጊዜ ከተማውን ስለፈጀው “እምቢ አልገዛም” ብሎ የኮበለለ ህዝብ ነው፡፡ ደርግ ከሰቆጣ የተባረረው ያኔ ነበር፡፡ ይሄ ህዝብ ፍቅሩ፣ መተሳሰቡና ትስስሩ ሁሉ የመጣው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ ያለ መንግስትም ኖረን ቆይተን ይሄ መንግስት ሲመጣ አካባቢውን ተቆጣጠረው፡፡ ያው የወጣበት፣ የተወለደበት ስፍራ በመሆኑ፣ እየመራ መጣ፤ እኛም እልል ብለን ተቀበልነው፡፡
ያለመንግስት ስትኖሩ እንዴት ነበር ህይወታችሁን የምትመሩት?
ጤፍ ከበለሳ በአህያ ተጭኖ ይመጣና ሌሊት እንገበያያለን፡፡ በቅሎው አህያው ሁሉ የሚሸጠው ሌሊት ነበር፡፡ መቼም የጋማ ከብቱ ያኔ ውድ ነው፡፡ ነገር ግን የከብቱ ዋጋ በጣም የወደቀ ነበር፤ ለመሸጥ እንኳን ስለማያዋጣ አይሸጥም፡፡ የምግብ እጥረት የነበረ ቢሆንም የተገኘውን በልተን ጠጥተን እናድራለን፡፡ ህዝቡ ከዚያ የተነሳ ነው ፍቅሩና መተሳሰቡን ያጠነከረው፡፡
በትግል ወቅት አህያ ትልቅ ሚና እንደነበራት ይነገራል...
አዎ… አህያማ በትጥቅ ትግሉ ወቅት አንዷ ታጋይ በያት፡፡ በረሃ ለበረሃ ትጥቅና ስንቅ ተጭና አብራ የምትጓዝ ባለውለታ ነበረች እንጂ፡፡ በቅሎ ደግሞ ለተጋዳላዮች ወደ ከተማ ሲመጡ ትረዳቸዋለች፡፡ እኛም የአህያንና የበቅሎን ስራ ያህል ከጫካ ወደ ከተማ ሲመጡ ተቀብለን እናግዛቸዋለን፣ ከአሰቡት እናደርሳቸዋለን፡፡
ገበያ ሌሊት የምትገበዩት ለምን ነበር?
ቀን ቀንማ ደርግ በአየር እየደበደበን ተቸገርን፡፡ “የእስላም መንደር” የሚባል ስፍራ አለ፤ ምሽግ ነው፡፡ በየሰው መኖሪያ ቤትም ምሽግ ነበር፡፡ የምንውለው ምሽግ ውስጥ ተደብቀን ነው፡፡ ይህቺ ከተማ እኮ በደርግ ዘመን አስራ አንድ ጊዜ በአየር ተደብድባለች፡፡ በቀን ሁለት ሶስት ጊዜ የምትደበድብበትም ጊዜ ነበር፡፡ አየር በላያችን ላይ ሲያንቧርቅብን፣ በሰማዩ ላይ ዞረው ዞረው አስጨንቀውን እኮ ነው የሚመለሱት፡፡
የሻደይን በዓል ለማክበር ሰቆጣ ከተማ ስንገባ የመንግስት ባለስልጣናት ያለአንዳች ጠባቂ ሲዘዋወሩ አይተናቸዋል፡፡ ይሄ እንዴት ሊሆን ቻለ?
ያለጠባቂ!?..የምን ጠባቂ ነው ደሞ የሚያስፈልጋቸው? ይሄ ህዝብ መስሎኝ ለዚህ ያበቃቸው፡፡ ከማን ይሸሸጋሉ? እና ዛሬማ ደርግ ጠላታቸው ወድቆ አይደል፡፡ እንኳን ሰቆጣ ይቅርና መላ ኢትዮጵያን ቢዞሩ ማን ይነካቸዋል..እንደው ለደንቡ ካልሆነ በቀር፡፡ እኔ አሁን ሰላምታ የሰጠኋቸው እነ ካሣ ተክለ ብርሃን፣ ታደሰ ካሣ፣ መዝሙር ፈንቴ፣ የተስፋዬ ገብረ ኪዳን ልጆችም አሉ፡፡ ምኑን እቆጥርልሻለሁ ልጄ፡፡ ባህርዳር ያለው ተጋዳላይ ሁላ የሰቆጣ ልጅ እኮ ነው፤ ያኔ ሳይጎለብቱ ከትምህርት ቤት የወጡ ናቸው፡፡
ከተማዋ እንደ ውለታዋ አልተደረገላትም የሚል ቅሬታ ይሰማል …
በዚህ በዚህ እኛም አሁን ያለውን መንግስት እናማዋለን፡፡ ልጆቻችን የተሰውትም ተሰውተው፣ በህይወት ያሉትም ለዚህ ደረጃ መድረሳቸው እሰየው ነው፡፡ ዛሬ “ብአዴን”፣ ቀደም “ኢህዴን” በሚል የሚጠሩቱ ልጆቻችን፣ ያሰቡትን ትግል አድርገው እዚህ መድረሳቸው ቢያስደስተንም ይሄ ነው የማይባል ችግር ውስጥ ነው ያለነው፡፡ መንገድ ያለመኖሩ፣ ለልጆቻችን በቂ ትምህርት ቤትና የጤና ተቋም ባለማግኘታችን እጅግ ተከፍተናል፡፡ ወደ ገጠሩ ወጣ ብለሽ ብታይ ደግሞ ልጄ…  አንቺው እማኝ ትሆኛለሽ፡፡
እርግጥ ነው..መብራት፣ ባንክ ቤት፣ ውሃ፣ ወፍጮ፣ ስልክ አለ፡፡ ሆኖም አካባቢው የተረሳና የተጣለ በመሆኑ፣ ህዝቡ ዛሬ ዛሬ ከፍቶታል፡፡

Published in ባህል

(Baaxo’gini baaxot yaagiteeh, baaxo abaara) -
የአፋር ተረት

የሚከተለውን የፃፉልን እጓለ ገብረ ዮሐንስ ናቸው፡፡ “የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ” በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ ነው፡፡
በግሪክ ሜቶሎጂ የሚገኝ አንድ ትልቅ ተረት አለ፡፡
(ይህም ስለ ፕሮሚሴቭስ የሚነገረው ነው፡፡ ትልቅ ምሥጢር በውስጡ ደብቆአል፡፡ ፕሮሚሴቭስ በሚል አርእስት የቀድሞውን ተረት መሠረት በማድረግ ኤስሂሎስ የሚባለው ትራጀዲን የፈጠረ ባለቅኔ፣ አንድ ትሪሎጂ - ማለት ሦስት ድራማዎች ጽፎአል፡፡ እሱን በመከተል ሸሊ ባይረን ጌቴ ጽፈዋል፡፡ የፕሮሚሴቭስ መንፈስ በአውሮፓ የመንፈስ ታሪክ ውስጥ መካከለኛውን መሥመር የያዘ ነው፡፡ አሁን የጠቀስናቸው ሰዎች በአውሮፓ የሥነ ጽሑፍ ጠፈር ላይ በጣም ጐልተው የሚታዩ ከዋክብት ናቸው፡፡)
የፕሮሚሴቭስ ተረት እንደሚቀጥለው ነው፡፡ ፕሮሚሴቭስ በከፊል አምላክ፣ በከፊል ሰው የሆነ ሕላዌ ነበር፡፡ በከፊል አምላክ እንደመሆኑ ዐሥራ ሁለቱ የግሪክ አማልክት በኦሉምቦስ ተራራ ሆነው ስለሰውና ስለዓለም አስተዳደር ሲመክሩ ይሰማ ነበር፡፡ በከፊል ሰው እንደመሆኑ የሰው ሥቃይና መከራ በጣም ያሳዝነው፣ ይጸጽተው ነበር፡፡ ሰው ቤት ንብረት ሳይኖረው በበረሃ፣ በጫካ፣ በዱር፣ በገደል፣ በዋሻ፣ በቁር፣ በሀሩር እንዲኖር ተፈርዶበት ነበር፡፡ ይህ መሆኑ አማልክት መክረው ዘክረው ለሰው የዕውቀት ምንጭ የሆነውን ብርሃንን የሰጡት እንደሆን ከዕለታት ባንድ ቀን ሰጭነታቸውን ክዶ በነሱ ላይ በመነሳት የሚያምፅ መሆኑን በመረዳት ብርሃንን ከሰዎች ደብቀው ከማይደርሱበት ቦታ በመሠወራቸው ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ሰዎች በጭለማና የርሱ ተከታይ በሆኑት ችግሮች ሥር ሲሰቃዩ ይኖራሉ፡፡
ይህ የሰዎች መራራ ዕድል ወገናቸው በሚሆን በፕሮሚሴቭስ ላይ ርህራሄ አሳድሮበት ብርሃንን አማልክት አርቀው ከደበቁበት ሰርቆ ለሰዎች ወስዶ ሰጠ፡፡ ያንጊዜ ማናቸውም ነገር ግልጽ ሆኖ ታያቸው፡፡ በብርሃን ምክንያት ጥበብና ማናቸውም የዕውቀት ስልት ስለተገለጸላቸው ራሳቸውን ከገዛ ራሳቸው በተገኘው ዘዴ ለማስተዳደር ጀመሩ፡፡
ፕሮሚሴቭስን ግን ለሰዎች ብርሃንን ሰጥቶ በጐ በመሥራቱ አማልክት ቀንተው በብርቱ ስቃይ ይቀጣ ዘንድ አዳኝ ከማይደርስበት ገደል ላይ ከቋጥኝ ድንጋይ ጋር በሰንሰለት ተቆራኝቶ አሞራ ለዘለዓለም እንዲበተብተው ፈረዱበት፡፡
***
ከፕሮሚሴቭስ ዕጣ -ፈንታ ይሰውረን፡፡ ይህ ፕሮሚሴቭስ የሰውን ዕድል ለማሻሻል የሚታገሉት የዕውቀት ሰዎች፣ የመምህራንና የሊቃውንት ምሳሌ ነው፡፡ እሱ ብርሃንን አማልክት ከደበቁበት ቦታ ወስዶ ለሰው እንዳበረከተ ፣ የዕውቀት ሰዎችም ዕውቀት በመለኮታዊ ምሥጢርነት ከሰው ተደብቃ ስትኖር ሳለ በብዙ ትግል አግኝተው፣ ከገዛ ራሳቸው አሥርፀው የወገኖቻቸውን ዕድል ለማሻሻል ያበረክታሉ፡፡ ዋጋቸውም ሌላ ሳይሆን ስቃይ መከራ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ሶክራቲስ በመርዝ ተገድሎአል፡፡ ጆርዳኖ ብሩኖ የጧፍ ቀሚስ ተጐናጽፎ በእሳት ተቃጥሎአል፡፡
እነዚህ ሰዎች እንደ ጧፍ መብራት ማለት ናቸው፡፡ ራሳቸው ነደው ተቃጥለው ያልቃሉ፡፡ ለሌሎች ግን ብርሃን ይሰጣሉ፡፡ የፕሮሜሴቭስ ምሳሌ አንድ ትልቅ ሕግ ጉልህ አድርጐ ያሳያል፡፡ ይህም “ዕውቀት በሥቃይ የሚገኝ ነው” (Learn through suffering) የሚል ነው፡፡  
ልጆቻችንን ይህን ለሌሎች ስንል መታገል፣ መሰዋት፣ ማድረግ እንደምን እናስተምር? ብርሃን የሚያመጡ ሰዎች ያስፈልጉናል፡፡ ዕውቀትን ለሀገር ለማጎናፀፍ የሚጥሩ መምህራን ያሹናል፡፡ የዕውቀት ብርሃን ለመጪው ትውልድ ታትሮ ለማለፍ ፣ ልብና ልቡና ይፈልጋል፡፡ አረፍ ብሎ ወዴት እያመራን ነው ብሎ መጠየቅን ግድ ይላል፡፡ ዕውቀት ከትምህርት ብቻ የሚገኝ አይደለም፡፡ ከኑሮአችን፣ ከልምዳችን፣ ከትግላችን እንጂ፡፡ ይህ ወረድ ብሎ አፈሩን መዳሰስን፣ ህዝቡን ማግኘትን፣ የልብ ትርታውን ማወቅን ይጠይቃል፡፡ ምን ጎደለው? ስለዚህ ጉዳይ ግንዛቤ አለ ወይ? በምን ዓይነት መንገድ የጎደለውን ዕውቀት ለማሟላት እችላለሁ? ማለትን ይጠይቃል፡፡ መንገዱን ካገኙ በኋላም፤ ጧት ማታ ሳይታክቱ መታተርን ይጠይቃል፡፡ ይህን ከልብ ካደረግን አገር መውደድ ገብቶናል፡፡ ያንድ ሰሞን ሞቅ ሞቅ ብቻ አገርን ከገባችበት ማጥ አያወጣትም፡፡ “ኦሆ በሀሊ፣ ያርጓጅ አናጓጅ፣ በደመቀበት ቦታ ሁሉ የሚያጨበጭብ አንድም የተለየ ነገር ለማስገኘት አይችልም” ይላሉ ዶክተር እጓለ፡፡ ሉቃስን በመጥቀስም እንዲህ ይሉናል፡- “ውሰብአ አቴናሰ ወእለ ይነግድ ኲሎሙ ህየ በእደ ትካዘ አልቦሙ ዘእንበለ ዳእሙ ለአፅምኦ ወነቢብ ዘሐዲስ”፡፡ አቴናውያን አዲስ ነገር ከመስማት ወይም ከመናገር በስተቀር ሌላ ምኞት አልነበራቸውም፡፡ ባለው ላይ ቆሞ አዲስ ነገር ለማግኘት የሚጣጣር ሰው ሁል ጊዜ ወደፊት ይሄዳል - ማለት ነው፡፡
እንደ አቴናውያን፤ በአለው ላይ ቆመን አዲስ ነገር ለማግኘት የምንጣጣር ከሆነ ወደፊት እንሄዳለን፡፡ ትምህርትንና ዕውቀትን መሰረቱ ያደረገ ትውልድ ከፈጠርን የራሱን ጥያቄ፣ የራሱን ነገ ራሱ ይወልዳል፡፡ የሚኖርበት ቤት ሲጠበው ቤቱን ራሱ አስፋፍቶ ይሰራዋል፡፡ ሁሉን እኛ እናድርግልህ ካልነው - ሁሉን ቀላቢ እንሁንለት ካልን፤ ዞሮ ዞሮ ተቀላቢ ትውልድ ነው የምናፈራው፡፡ ፈረንጆቹ እንደሚሉት - Spoon – Feeding mentality ይጠቀልለዋል - የአጉሩሱኝ አስተሳሰብ እንደማለት ነው፡፡
ለወጣቱ የመንግሥቱ ለማን ግጥም “መርፌ - ትሰራለህን” ማንበብና በዚያ አቅጣጫ መጓዝ የአባት ነው በየትኛውም አቅጣጫ! ወጣቱ በሥነ ምግባር ረገድ፣ የሰውን ፀባይና ችሎታ በሚመረምር መልኩ አዕምሮው መታነፅ አለበት፡፡ ዕውቀትን መሰረት ሳያደርግ ለትግል ብቻ ብናዘጋጀው የፕሮፖጋንዳ ወይም የአጀንዳ ማስተላለፊያ አሸንዳ ቱቦ ነው የሚሆነው፡፡ ይህ በታሪክም የታየ ነው፡፡ በማህበራዊ ኑሮው የእያንዳንዱ መብትና ተግባር የሚጠበቅበት፣ “ሰው በንፁህ ተምኔቱ መሰረት በሰላም ተደስቶ የሚገኝበትን ሕግ” ይዞ መጓዝ እንዳለበት ሊረዳ ይገባል፡፡ ህይወት እንደ ጂኦሜትሪ ትምህርት በቀጥታ መሥመር የተሞላና የተለካ አይደለም፡፡ ቀላል ሂሳብም አይደለም፡፡ እንዴት እንደሚገነባ፣ ከራሱ ህይወት ተነስቶ እንዴት ለማደግ እንደሚችል፣ ትምህርትን ባሰላሰለ መልኩ ማጤን እንጂ “ሳይገሉ ጎፈሬ፣ ሳያረጋግጡ ወሬ” መሆን የለበትም፡፡ እስከዛሬ አጭር ተመልካች፣ አጭር ተጓዥ ሳናደርገው (Myopic) አልቀረንም፡፡ አጭር ግቦች አጭር ያደርጉናል!
አንድ ደራሲ እንደሚለው፤ “… የውጪ ጉዳዮችን ካገር ውስጥ ኃይሎች አሰላለፍ፣ ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ከጥበብ ሽግግርና ከውጪ ርዳታ፣ የቋንቋ መዘበራረቅና ጉራማይሌነትን ከባህላዊ ድቀት፣ የሐሳብ ነፃነትን ከጋዜጣ፣ ራዲዮና አጠቃላይ ውይይት ምህዳር መጥበብ ጋር…” የሚያነፃፅር ወጣትም ሆነ አዋቂ ያስፈልገናል፡፡
ወጣቱ አገሩን ያውቅ ዘንድ ጥልቅ አስተሳሰብ፣ ረዥም ርዕይና በግብረገብ የታነፀ ድፍረትና መስዋዕትነት ያስፈልገዋል፡፡ መጪውን አዲስ ዓመት እንዲህ እናስብ! የሀገራዊነት፣ የወገን አሳቢነት፣ የኢ-ራስ - ወዳድነት፣ የሁሉን - አውድም አስተሳሰብ አለመያዝ፣ ሁሉን - ረጋሚ ያለመሆን አመለካከት፣ ኢፅንፋዊነት ወዘተ እንደመርህም፣ እንደኑሮም ሊሰርፁበት ይገባል፡፡ አለበለዚያ አፋሮች እንደሚሉት “አገሩን የማያውቅ ሰው፣ መሬትን እየረገጠ መሬትን ይረግማል” ይሆናል፡፡                 



Published in ርዕሰ አንቀፅ
Page 2 of 20