የሃይማኖት መሪው ቡድሐ የሚሰጠን አንድ ዕንቆቅልሽ የሚከተለውን ይመስላል፡፡
አንድ ነጋዴ ሩቅ አገር ሄዶ ሲመለስ፤ ቤቱ በሽፍቶች ተዘርፎና ተቃጥሎ ይደርሳል፡፡
ከቤቱ የተረፈው ረመጥ - መካከል አንድ ተቃጥሎ የከሰለ የሰው ገላ ያያል፡፡ “ይሄ ትንሹ ልጄ መሆን አለበት” አለ፡፡
በዚህ ምክንያት ምርር ብሎ አለቀሰ፡፡ ደረቱን መታ፡፡ ፀጉሩንም ነጨ፡፡
ገላውን እንደገና የማቃጠል፤ የሐዘን ሥነስርዓት እንዲካሄድም አደረገ፡፡
ይህ ወንድ ልጁ ነው፡፡ ከልጁ የናፍቆት ስሜት ለመላቀቅ በጭራሽ ካለመፈለጉ የተነሳ፣ ለቅጽበት እንኳ ሳይለየው የልጁን አስከሬን አመድ በከረጢት አንጠልጥሎ ይዞር ጀመር፡፡ ቆይቶም ከሀር የተሰራ ከረጢት አሠርቶ ይሸከመው ጀመር፡፡ ቀን ከሌት ይዞት ይዞራል፡፡ ሥራም ቦታ ቢሆን ተሸክሞት ይውላል፡፡ በእረፍት ሰዓቱም እንደዚያው፡፡ ከአመዱ የሚለይበት አንዳችም ደቂቃ የለም፡፡
አንድ ሌሊት፤ ለካ ወንድ ልጁን ሽፍቶቹ አግተው ወስደውት ኖሮ፤ ከታሠረበት አምልጦ አባቱ አዲስ ወደ ሠራው ቤት ይመጣል፡፡
ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ላይ ደርሶ፤ የአባቱን ቤት በር በስሜት ፍንድቅድቅ ብሎ አንኳኳ፡፡
አባቱ፤ አሁንም የከረጢት አመዱን እንደተሸከመ ነው፡፡
“ማነው፤ በዚህ ሌሊት የሚያንኳኳው?” አለና ጮኾ ጠየቀ፡፡
“እኔ ነኝ - ወንድ ልጅህ ነኝ አባባ”፤ አለ ልጁ በበሩ ሽንቁር እያየ፡፡
“አንተ ባለጌ ሰው፡፡ አንተ የእኔ ልጅ ልትሆን ከቶ አትችልም፡፡ የእኔ ልጅ ከሶስት ወር በፊት ሞቷል፡፡ አመዱ እዚሁ እጄ ውስጥ አለ!” አለው፡፡
ትንሹ ልጅ ግን በሩን መደብደቡን ቀጠለ፡፡ ጮኾ፤
“ኧረ አባባ እኔ ያንተው ልጅ፣ የምታውቀኝ ውዱ ልጅህ ነኝ፤ አስገባኝና እየኝ!” ደጋግሞ ለመነው፡፡ ተማጠነው፡፡
አባትዬው ግን፤
“ዘወር በል ብዬሃለሁ! ከዚህ ወዲያ አልታገስህም፡፡
ድራሽህ ይጥፋ! አለዚያ ብትንትንህን ነው የማወጣህ” ለመጨረሻ ጊዜ ልንገርህ፤
የእኔ ልጅ በሽፍቶች ተቃጥሎ ሞቶ፣ እኔ አስከሬኑን አመድ አድርጌ፣ አመዱን ተሸክሜ ስዞር ከርሜያለሁ፡፡ ስለዚህ አንተ የመጣኸው የልጄን ሐዘን ዳግመኛ ለመቀስቀስና የእኔን አንጀት ለማቃጠል ነው! አንት ጨካኝ አረመኔ፤ ጥፋ ከፊቴ!”
ልጅየው ተስፋ ቆርጦ ሰፈሩን ጥሎ ጠፋ፡፡
አባት፤ በህይወት ያለ ዕውነተኛ ልጁን ለአንዴም ለዘለዓለም አጣ፡፡
* * *
እንደ ቡድሐ አመለካከት፤ ከአንድ አስተሳሰብ ጋር እኝኝ ብለን ከተጣበቅንና፤ “አንዱና አንዱ ዕውነት” ይሄ ብቻ ነው ብለን ካከረርን፣ ዕውነተኛውን ዕውነት የማወቅ ዕደላችንን እንዘጋለን። ዕውነት እንደሰው ደጃፋችሁ ቆሞ ቢያንኳኳም እንኳ የአዕምሮአችሁን በር ለመክፈት ዝግጁ አትሆኑም፡፡ ስለዚህ ስለ አንድ ዕውነት የምትገነዘቡበትን መንገድ ሥራዬ ብላችሁ መርምሩት፡፡ ተጠንቀቁ፡፡ የነገር ሁሉ መጀመሪያው፤ ከሃሳብ እሥር ነፃነትን ማወጅ ነው፡፡
ይህን ዕውነት ወደ እኛ አገር ፖለቲካ ስንመነዝረው፤ ቁልጭ ያሉ፤ አመድ የማቀፍና ህያው ልጅን የመካድ፤ ዕውነታን እናገኛለን፡፡
ዕውነተኛውን ልጃችንን እንለይ፡፡ በከረጢት ውስጥ ያለው አመድ በህይወት ካለው ልጅ የተለየ መሆኑን እርግጠኛ እንሁን፡፡ ከአመዱ - ከግትር ሃሳባችን፣ እንገላገል፡፡ እኛ የጀመርነው መንገድ ብቻ ነው ዳር የሚያደርሰው ብለን ድርቅ ከማለት አባዜ ተላቀን፤ የጀመርነው መንገድ መጨረሻ የማያሳልፍ - ግድግዳ (Dead End) ቢሆንስ? አብረውን ከሚጓዙት መካከል ሃሳባቸውን የሚለውጡ ቢገኙስ? የመኪናው ጐማ ቢተነፍስስ? የባቡሩ ሃዲድ ቢጣመምስ? ብለን እንጠይቅ። አንድ የአገራችን ፀሐፌ ተውኔት እንዳለው፤
“ገና ላልተወለደ ልጅ ስም እናውጣ ብለን ለምን እንጣላለን፡፡ “ዐይናማው” ብለነው ዕውር ሆኖ ቢወለድስ? ክንዴ ብለነው እጁ ቆራጣ ቢሆንስ?...” ብለን መጠራጠር ቢያንስ ከጭፍንነት ያድነናል። ከአንድ መሥሪያ ቤት በሙስና፣ በፍትሐዊነት ወይም በኢዲሞክራሲያዊነት፤ በግምገማ የተነሳን ሰው ለሌላ መሥሪያ ቤት በኃላፊነት ማስቀመጥ አልሸሹም ዞር አሉ፤ ነው፡፡ ይሄኛው መሥሪያ ቤት አንቅሮ የጣለውን ግለሰብ ያኛው መሥሪያ ቤት በምን ዕዳው ይሸከማል? የሀገሪቱን የሥራ ሂደት ባለቤቶች በበኩር ልጅነት አቅፈንና “የባለቤቱ ልጅ” አሰኝተን ስናበቃ፤ በሀቅ የሚለፉላትን ሀቀኛ ልጆች በር እያንኳኩ ሳንከፍት እያባረርናቸው ምን ዓይነት ለውጥ ማምጣት ይቻለናል? በቡድናዊና ድርጅታዊ መንፈስ፤ እስከመቼ እከክልኝ ልከክልህ ተባብለን እንዘልቀዋለን?
“ዕብድ ሆኜ ስለማላውቅ፣ ዕብድ የሚያስበውን አላውቅም፡፡ ዝም፣ ጭጭ ብለህ ተቀምጠህ ሳይህ፣ ምናልባት ይሄ ዕብደትህ ልዩ ሰላም ሰጥቶህ ይሆንን? ብዬ እቀናብሃለሁ-መንሳፈዊ ቅናት ማለቴ ነው” ይላል የአገራችን ፀሐፊ፡፡ ዝምታ ማስቀናቱ ይገርማል፡፡ ስንት ግፍ ሲሰራ እያየህ ዝም። ስንት ዘረፋ ሲካሄድ እያየህ ዝም፡፡ ጓዳህ እየተራቆተ፣ ኢኮኖሚህ እየተንኮታኮተ እያየህ ዝም ለማለት ከቻልክ፣ የሚያስቀና ዝምታ አለህ፤ ታድለሃል፤ ማለት ነው፡፡ ከዕብደት ውስጥ የሚገኘው ልዩ ሰላም ይሄ መሆኑ ነው፡፡ ዝም የሚሉ ያሉትን ያህል፣ ሃያ አራት ሰዓት በመለፍለፍ እኛ ነን ጀግና የሚሉም አገራችን ያፈራቻቸውና በተገለባባጭነት፣ በአድር ባይነት፣ በጥገኝነት ንፍቀ - ክበብ ውስጥ የሚኖሩ አያሌ “ቀልጣፋ” ሰዎች አሉ፡፡ ከጠቆረው መጥቆር፣ ከነጣው መንጣትን ተክነውበታል፡፡
“እንደወዶ -ገባ ኮርማ፣ ተነስ ሲሉት የሚነሳ፤
ተኛ ሲሉት የሚተኛ!”
ያለው ዓይነት ነው ገጣሚው፡፡ ከየትኛውም ማዕድ ለመቋደስ እጃቸውን (የዓለም የእጅ መታጠብን ቀንን እያከበረ እንደማለት) ታጥበው፣ ዝግጁ ሆነው የሚጠብቁ ናቸው፡፡ ለእነሱ ፖለቲካ በየትኛውም የሳንቲሙ ገጽ - ማለትም በአውሬውም በሰዉም በኩል - ለመጠቀም የሚችሉ ናቸው፡፡ መቼም ቢሆን መቼም በየትኛውም ገዢ ዘመን አድርባይነታቸውን አያቋርጡም። The pendulum of opportunism never stops oscillating እንዳለው ነው ሌኒን፡፡ “ከአህያ ጋር ብጣሪ በልታ፣ ከፈረስ ጋር ገብስ ትበላለች” ይለዋል የወላይታው ተረት፡፡ ከአድባርባይነት እርግማን ይሰውረን!

Published in ርዕሰ አንቀፅ

“ፍርሃትን፣ ሙስናን፣ አፈናን፣ አምባገነንነትን በጋራ በቃ ካልን፣ ያበቃል”
ለአገሪቱ ችግሮች የጋራ መፍትሔ ለማፈላለግ 33 ተቃዋሚ ፓርቲዎች በጥምረት ኮሚቴ አደራጅተው እየሰሩ መሆናቸውን የገለፁት የኮሚቴው አስተባባሪ አቶ አስራት ጣሴ፤ ፓርቲዎቹ ነገ በመኢአድ ጽሕፈት ቤት “በቃ እንበል” የተሰኘ ህዝባዊ ስብሰባ እንደሚያካሄዱ አስታወቁ፡፡
ለህዝባዊ ስብሰባው “በቃ እንበል” የሚል መሪ ቃል ለምን እንደተመረጠ አቶ አስራት ሲያስረዱ፣ ህዝቡ የአገሪቱን ችግሮች የማስቆምና የማስወገድ አቅም እንዳለው የሚያሳይ አባባል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ህዝቡ ምን ቢያደርግ ችግሮችን መፍታት እንደሚችል መወያየትና መላ ማበጀት የስብሰባው አላማ እንደሆነ አቶ አስራት ጠቅሰው፤ ችግሮችን ለማስወገድ “በቃ እንበል” የሚል አቋም እንደያዙ ተናግረዋል፡፡
ገዢዎቻችን ፍርሃት ይፈጥሩብናል፤ ነገር ግን በጋራ “በቃ” ካልን ያበቃል፤ እናም በሰላማዊ ትግል የመብታችን ባለቤት እንሆናለን ብለዋል-አቶ አስራት፡፡ ሙስናን በጋራ በቃ ካልን፣ ሙስና አብቅቶ ጤናማ የስራና የንግድ ውድድር ይፈጠራል በማለትም ስብሰባው የአገሪቱ ዋና ዋና ችግሮችን እንደሚዳስስ አስረድተዋል፡፡
ኢፍትሃዊነትንና ውርደትን በጋራ በቃ ካልን ያበቃል፤ ፍትህ ከመንበሯ ላይ ተቀምጣም ክብራችን ይመለሳል ያሉት አቶ አስራት፤ በእምነት ነፃነት ላይ ጣልቃ መግባትንና በሽብር ስም በሀሰት መወንጀልን በቃ ካልን ያበቃል፤ መብታችን ይከበራል፤ እንደየእምነታችንም በነጻ እናመልካለን ብለዋል፡፡ በጥምረት እየሰሩ ያሉት 33ቱ ፓርቲዎች በጋራ የሚሰሩት ይህን አቋም በመያዝ እንደሆነም አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡ የገዢውን ፓርቲ የዘረኝነት፣ የመከፋፈልና የማጋጨት ፖሊሲ በቃ ካልን ያበቃል፣ በምትኩም ትብብር ይነግሳል ሲሉ የፓርቲዎቹን አቋም የገለፁት አቶ አስራት፤ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አጃቢ ማድረግ በቃ ካልን ያበቃል፤ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት እውን ይሆናል ብለዋል፡፡ ነፃ ፕሬስ አፈናንና እስርን በጋራ በቃ ካልን፤ በነፃነት እንነጋገራለን፤ አማራጭ የመረጃ ምንጮችን ከእጃችን እናስገባለን ካሉ በኋላ፣ እሁድ እለት ከህዝቡ ጋር በአንድነት “በቃ” የምንልበትን ቀጠሮ ይዘናል ብለዋል፡፡ እነዚህ ሃሳቦች ተግባራዊ ከሆኑ፤ ኢህአዴግን ጨምሮ ሁሉም በእኩልነት የሚተዳደሩባትን ሀገር መፍጠር እንችላለን ያሉት አቶ አስራት፤ ዝግጅቱ ላይ ከ1500 በላይ ሰው እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ ስብሰባው በፓርቲ ፅ/ቤት ለማድረግ የተወሰነው ፍቃድ ጠይቁ በሚል ሰበብ እንዳይስተጓጎልብን ነው ብለዋል፡፡

Published in ዜና

“ያከራየኋቸውን ቤት ለመልቀቅ እምቢተኛ ስለሆኑ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሳውቄያለሁ”
- ኢ/ር ኃይሉ

ኖርዌይ ኤምባሲ ከኢ/ር ኃይሉ ሻውል የተከራየውን ባለ ሁለት ፎቅ የመኖሪያ ህንፃ ለ15 አመታት ሲጠቀምበት እንደቆየ የገለፁት የአዲስ አድማስ ምንጮች፣ በሁለቱ ወገኖች መካከል ውዝግብ የተፈጠረው ቤቱን ልቀቅ፣ አልለቅም በሚል ነው ብለዋል፡፡ በ97 ምርጫ የምርጫ ዘመቻ ቅንጅትን በፕሬዚዳንትነት የመሩት ኢ/ር ኃይሉ ሻውል፣ ከኤምባሲው ጋር በነበራቸው የኪራይ ውል መሰረት ከ7 ወራት በፊት ቤቱን እንዲያስረክባቸው እንደጠየቁ ተናግረዋል፡፡ በ3200 ካሬ ሜትር ግቢ ውስጥ የተሰራው ባለ ሁለት ፎቅ መኖሪያ ህንፃ በ1200 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ነው፡፡
ቤቱን ስለምንፈልገው ልቀቁልን በማለት ከሰባት ወራት በፊት በደብዳቤ ብንጠይቅም፤ ኤምባሲው ለመልቀቅ ፈቃደኛ አልሆነም የሚሉት ኢ/ር ሃይሉ፣ ከአንድ አመት በፊትም ኤምባሲው ቤቱን እለቃለሁ ቢልም ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል ብለዋል፡፡ “ቤቱን በትክክል ከፈለጋችሁት ግዙን” በማለት ለኤምባሲው አማራጭ አቅርበው ተቀባይነት እንዳላገኘም ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ጉዳዩን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማሳወቃቸውን ኢ/ር ኃይሉ ጠቅሰው፣ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ኤምባሲው ቤቱን እንዲለቅ ጥያቄ አስተላልፏል ብለዋል፡፡
“ህግና ስርዓትን ተከትዬ ቤቱን እንዲለቁ በትዕግስት ጠብቄያለሁ፡፡ እምቢ ካሉ በግል ንብረቴ ከእነርሱ ጋር እንካ ሰላንቲያ አልገጥምም” ያሉት ኢ/ሩ፤ ጥቁርን በመናቅና በማን አለብኝነት የሚካሄደውን ህገወጥነት ፈፅሞ አልቀበልም ብለዋል፡፡ ኤምባሲው የያዘብኝ ቤት ከመኖሪያ ቤቴ ጋር በአጥር ስለሚገናኝ በቤቴ በኩል አፍርሼ በመግባት ግቢውን ለማስተካከል ወስኛለሁ ብለዋል ኢ/ር ኃይሉ፡፡ ወደ ኤምባሲው በተደጋጋሚ ደውለን ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ምክትል አምባሳደሯን ለማነጋገር ብንሞክርም “አሁን ቴሌ ኮንፈረንስ ላይ ነኝ፤ ማናገር አልችልም” የሚል ምላሽ በፀሀፊያቸው በኩል ተናግረው፤ መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡
ስለዚሁ ጉዳይ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፕሮቶኮል ክፍል ደውለን ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ሀላፊ ለማግኘት ሙከራ ብናደርግም ለስብሰባ ከግቢ ውጭ ናቸው በሚል ምላሽ ልናናግራቸው አልቻልንም፡፡

Published in ዜና

አዲስ አበባ ውስጥ ጣና አፓርትመንት ተብሎ በሚታወቀው መኖሪያ ህንፃ፣ በቤት ሰራተኝነት ተቀጥራ ከገባች ወር ያልሞላት ወጣት ባለፈው ረቡዕ ማታ ከ4ኛ ፎቅ ወድቃ ሆስፒታል ገባች፡፡ የ16 አመቷ ቅንነት ጎዳኔ ከፎቁ ከመውደቋ በፊት አሰሪዋ ይዛት እንደነበረ የተጐጂዋ ዘመድ ተናግራለች፡፡ አሰሪዋ በተጠርጣሪነት እንደታሰረች ለማወቅ ተችሏል፡፡
ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባት ቅንነት፣ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላት ቢሆንም እስካሁን የመናገር አቅም አላገኘችም፡፡
በቤት ሰራተኝነት ከተቀጠረች ገና ሃያ ቀኗ ነበር ያለችው የአክስቷ ልጅ መዓዛ ጥጋቡ፤ ዋስ ሆና እንዳስቀጠረቻት ገልፃ፣ ከፎቅ ስትወድቅም በቦታው እንደነበረች ትናገራለች፡፡ አሰሪዋ ረቡዕ ማታ ደውላ እንደጠራቻትና ቶሎ ነይ እያለች በተደጋጋሚ እንደደወለችላት መዓዛ ገልፃለች፡፡ በቦታው ስደርስ፣ አሰሪዋ በጩኸት የጥበቃ ሰራተኛውን እየተጣራች ነበር የምትለው መዓዛ፣ ከጥበቃ ሰራተኛው ጋር ተሯሩጠን ስንገባ፣ ቅንነት ከፎቁ ላይ ተንጠልጥላ፣ አሰሪዋ እጇን ይዛ አየሁ ትላለች፡፡ ብዙም ሳይቆይ ለቀቀቻትና ወደቀች የምትለው መዓዛ፤ ቅንነት አሰሪዬ መጥፎ ፀባይ አላት በማለት ነግራት እንደነበር ገልፃለች፡፡ ፖሊስ ጉዳዩን እየመረመረ ሲሆን በቦሌ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ በእስር እንድትቆይ የተደረገችው አሰሪዋ፤ሰኞ ፍርድ ቤት ትቀርባለች ተብሏል፡፡

Published in ዜና

“ወደ ስፍራው ከመድረሳቸው በፊት ጥበቃ እንዲደረግላቸው አላሳወቁም”
- (የዞኑ ኦህዴድ ጽ/ቤት)
አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ (አንድነት) ነገ በፍቼ ከተማ የሚካሄደውን ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ ለማስተባበር በስፍራው የተገኙት ሁለት አባላቱ መደብደባቸውን አወገዘ፡፡ የፓርቲው የህግ ክፍል ድርጊቱን በፈፀሙ አካላት ላይ ክስ ለመመስረት ወደ ስፍራው እንደሚጓዝ ተገልጿል፡፡
የአንድነት ፓርቲ የአዲስ አበባ የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ አቶ ነብዩ ባዘዘው እና ባልደረባቸው አቶ መሳይ ትኩ፤ ነገ የሚካሄደውን ሰላማዊ ሰልፍ ለማስተባበርና አንዳንድ ዝግጅቶችን ለማድረግ ረቡዕ አስር ሰዓት ተኩል አካባቢ ፍቼ ከተማ መድረሳቸውን የገለፁት የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ዳንኤል ተፈራ፤ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ገደማ ባረፉበት ሆቴል በከተማው የፀጥታ ዘርፍ ምክትል ሃላፊና ሌሎች ፊታቸውን በሸፈኑ 11 ሰዎች ከፍተኛ ድብደባ እንደደረሰባቸውና ራሳቸውን ሲስቱ ጥለዋቸው መሄዳቸውን ገልፀዋል፡፡ “በስፍራው የደረሰው ፖሊስ ህገ ወጥ ድርጊት የፈፀሙትን ይዞ ወደ ህግ ማቅረብ ሲገባው፣ ዱላቸውን ቀምቶ ወደቤታቸው መሸኘቱ አይን ያወጣ የህግ ጥሰት ነው” ያሉት አቶ ዳንኤል፤ በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀስ ህጋዊ ፓርቲ አባላትን በዚህ መልኩ ማሰቃየቱ የህግ የበላይነት እየተጣሰ መሆኑን ያመላክታል ብለዋል፡፡
ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድና ክስ ለመመስረት የፓርቲው የህግ ክፍል ወደዞኑ እንደሚያመራም አቶ ዳንኤል በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡
አንድነት የጀመረው የሶስት ወር የህዝብ ንቅናቄ አካል የሆነውን ሰላማዊ ሰልፍ ነገ በባሌ ሮቤ፣ በአዳማና በፍቼ ለማከናወን እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ዳንኤል፤ ይህን እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ የፍቼ ከተማ የፀጥታ ዘርፍ ሃላፊዎችና ግብረ አበሮቻቸው ያደረሱትን ህገ-ወጥ ድርጊት ፓርቲው በቸልታ እንደማያልፈው ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ድብደባ ተፈፀመባቸው ወደተባሉት አቶ ነብዩ ባዘዘው ደውለን በሰጡን መረጃ፤ የከተማው የፀጥታ ዘርፍ ም/ሃላፊ የሆኑት አቶ ሃይለየሱስ በየነና ሌሎች 11 ሰዎች እንደደበደቧቸው ገልፀው፤ “በመጀመሪያ እኛ የያዝነውን አልጋ ካልያዝኩ የሚል አንድ ሰው ልከው ነገር ፈለጉን፤ ግን እኛ ዝም አልን” ብለዋል፡፡
የሆቴሉ ባለቤቶች “መጀመሪያ አከራይተነዋል፤ አሁን ለመጣ ሰው እንዴት እንሰጣለን” በሚል በተነሳ ክርክር፣ የፀጥታ ዘርፍ ሃላፊው እና ግብረ አበሮቻቸው ከፍተኛ ድብደባ እንዳደረሱባቸው የተናገሩት አቶ ነብዩ፤ እነዚህ ሰዎች ደብድበዋቸው ከሄዱ በኋላ ፖሊሶች ወደመኝታቸው ገብተው የፓርቲውን የፍቃድ ወረቀት፣ መታወቂያቸውን፣ ቃለ ጉባኤና ሌሎች ቁሳቁሶችን በመውሰዳቸው ምንም አይነት ስራ ለመስራት መቸገራቸውን ጠቁመዋል፡፡ በድብደባው እሳቸውም ሆኑ ባልደረባቸው ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ጠቁመው፤ ባልደረባቸው አቶ መሳይ ትኩ በግራ እጃቸው ላይ ስብራት እንደደረሰባቸው ሀኪሞች መናገራቸውን ገልፀዋል፡፡
የሰሜን ሸዋ ዞን የኦህዴድ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ሰለሞን መኮንን ጋር ቀርበው ልብሳቸውን በማውለቅ የደረሰባቸውን ጉዳት ማሳየታቸውን የተናገሩት አቶ ነብዩ፤ ሃላፊው ይህ ህገ ወጥ ድርጊት ነው፤ ፓርቲያችንም ሆነ መንግስታችን አይቀበለውም፤ በአስቸኳይ ኮሚቴ አቋቁመን ድርጊቱን የፈፀሙ ግለሰቦች ላይ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እንወስዳለን፤ እናንተም ክስ መስርቱ ብለውን ይህን እያደረግን ነው ብለዋል፡፡
“ፖሊሶችም፤ ደብዳቤዎቹን ወደ ህግ ሳያቀርቡ በሰላም መሸኘታቸው በፓርቲያችን ላይ ሆን ተብሎ የተቀነባበረ ሴራ እየተፈፀመ መሆኑን ማሳያ ነው፤ እኛ ግን ሰላማዊ ትግላችንን እንቀጥላለን” ብለዋል አቶ ነብዩ፡፡
በሰሜን ሸዋ ዞን የኦህዴድ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ሰለሞን መኮንን በበኩላቸው፤ ጉዳቱ የደረሰባቸው የአንድነት ፓርቲ ሰዎች ቀደም ብለው ወደ ከተማው ስለመምጣታቸው ለኦህዴድ ጽ/ቤትም ሆነ ለፀጥታ አካሉ አለማሳወቃቸውን ገልፀው፤ ይህን ቢያደርጉ ኖሮ ጥበቃ ሊደረግላቸው ይችል እንደነበር አብራርተዋል፡፡
“በተፈፀመው ድርጊት እንደግለሰብም እንደ መንግስት አመራርም በጣም አዝኛለሁ” ያሉት የጽ/ቤት ሀላፊው፤ ጉዳቱን ያደረሰባቸው አንድ ግለሰብና የባጃጅ ሹፌር እንደሆነ መስማታቸውንና ይህም ግለሰብ በሀገሪቱ ህግ መሰረት ተጠያቂ እንደሚሆን ገልፀዋል፡፡
የፀጥታ ዘርፍ ም/ሀላፊውና ሌሎች የፖሊስ አካላት የፓርቲውን አባላት ደበደቡ የተባለውን ግን አቶ ሰለሞን አስተባብለዋል፡፡ የማሳወቂያ ደብዳቤውን በተመለከተ፤ ሰዎቹ ለከተማው ከንቲባ ጽ/ቤት ያስገቡት ችግሩ ከተፈጠረ በኋላ መሆኑን ከከንቲባው ጽ/ቤት መስማታቸውንም ሀላፊው አብራርተዋል፡፡
“ያስገቡት ደብዳቤ ፎርማሊቲውን ያሟላ አያሟላ ባላውቅም ደብዳቤው መስፈርቱን አሟልቶ ሰልፉ ከተፈቀደ የፀጥታ አካሉ ጥበቃ ያደርግላቸዋል” በማለት አረጋግጠዋል፡፡ መደብደባቸውን ከተናገሩ በኋላ ጥበቃ እየተደረገላቸው መሆኑን ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ጉዳት የደረሰባቸው የፓርቲው አባላት ድብደባውን በፈፀሙ ግለሰቦች ላይ መረጃ አሰባስበው ክስ መመስረት እንደሚችሉም አቶ ሰለሞን ገልፀዋል፡፡

Published in ዜና

“መረጃው የተሳሳተና ከእውነት የራቀ ነው” የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዝዳንት

ዘንድሮ ብቻ በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት በዳኝነት ሙያ ያገለግሉ የነበሩ መቶ ዳኞች ስራ መልቀቃቸውን ምንጮች ገለፁ፡፡ ከ86 በላይ ዳኞችም የመልቀቂያ ደብዳቤ አስገብተው መልስ እየተጠባበቁ እንደሆነ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ የኔነህ ስመኝ በበኩላቸው፤ መረጃው የተሳሳተና ከእውነት የራቀ ነው ሲሉ አስተባብለዋል፡፡ “እንደማንኛውም መስሪያ ቤት አንዳንድ መልቀቂያዎች ይገባሉ፤ ይስተናገዳሉ” ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ በተጠቀሰው መጠን ዳኞች ስለመልቀቃቸውም ሆነ መልቀቂያ ስለማስገባታቸው የማውቀው ነገር የለም ብለዋል፡፡
ዳኞቹ በደሞዝ ማነስ ፣በጥቅማጥቅም ማጣት፣በእርከን እድገት አለመኖርና በስራቸው ላይ በሚደርስባቸው ጣልቃ ገብነት ከስራ ለመልቀቅ መገደዳቸውን ምንጮቹ ገልፀው፣ በቅርቡ የገቡ መልቀቂያዎች ከሶስት ወር በፊት እንደማይስተናገዱ እየተነገራቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ “በክልላችን የዳኛ ደሞዝ ከፖሊስ ደሞዝ ያንሳል” ያሉት አንድ ስራ የለቀቁ ዳኛ፤ የፖሊስ የስራ ሂደት 2800 ብር ደሞዝ ሲያገኝ ዳኛ ግን 2639 ብር ብቻ እንደሚያገኝ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
የዳኝነት ስራ የህሊና ስራ እንደመሆኑ አንድ ዳኛ ለአድልኦና ለጉበኝነት እንዳይጋለጥና ፍትህ እንዳያዛባ ምቹ ሁኔታዎች ሊፈጠሩለት ይገባል ያሉት ምንጮቹ፤ በክልሉ ይህ ስለማይመቻች ፍትህ ከማዛባት ስራውን መልቀቅና መቸገር ይሻላል በሚል ዳኞች ስራ እንደለቀቁና ሌሎችም ለመልቀቅ ማመልከቻ እያስገቡ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
ም/ቤቱ የዳኞች በብዛት መልቀቅ ስላሳሰበው ስብሰባ ካደረገ በኋላ ዳኞች በስራቸው ላይ እንዲቆዩ ጭማሪ ይደረግላቸው ብሎ መወሰኑን የጠቆሙ ሌላ ሥራ የለቀቁ ዳኛ፤ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ላሉት 500 ብርና ከዚያ በላይ ሲጨመርላቸው ታች ሆነው ብዙ ለሚሰሩትና ለሚደክሙት ግን በ150 ብር ጭማሪ ብቻ መሸንገላቸው ዳኞችን አበሳጭቷቸዋል ብለዋል፡፡ ይህም ለመልቀቃቸው ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ፍ/ቤቱ በየአመቱ ከስልጠና ማዕከል የሚወጡ ዳኞችን እንደሚቀበል የገለፁት ምንጮቹ፤ እነዚህ ዳኞች ሲቀጠሩ በፍ/ቤት ሁለት አመት የማገልገል ግዴታ እንዳለባቸውና ሁለት አመቱን ሳይጨርሱ ከለቀቁ 50 ሺህ ብር እንደሚቀጡ ጠቁመው፤ ሙያተኛው ላይ የሚደረግ ጫና መቆም አለበት ሲሉ ተናግረዋል፡፡ “ከሙያው ስነ-ምግባር የተነሳ ዳኛ ትርፍ ስራ መስራት አይችልም” ያሉት እነዚሁ ዳኞች፤ በዚህ የተነሳ የዳኛው ህይወት ከኑሮ ውድነቱ ጋር መጣጣም አልቻለም ብለዋል፡፡ በሌላው የመንግስት መስሪያ ቤት የተለያዩ ማበረታቻዎችና የደሞዝ እርከን ጭማሪ እንደሚደረግ ጠቁመው፣ በፍ/ቤት አካባቢ ይህ አይነት አሠራር የለም፣ አስር አመት የሰራም ሆነ ዛሬ የተሾመ ዳኛ እኩል ደሞዝ ነው ያላቸው ብለዋል፡፡

Published in ዜና

ንብ ኢንተርናሽል ባንክ እና ንብ ኢንሹራንስ ኩባንያ ባለ 35 ፎቅ ህንፃ መሠረት ለማስገባት ከቻይናው “ሬይል ዌይ ነምበር ስሪ” ኩባንያ ጋር ተፈራረሙ፡፡
የሁለቱ እህትማማቾች ድርጅት ዋና መ/ቤት ህንፃ የሚገነባው ከብሄራዊ ቴያትር ጀርባ ነው፡፡
በአሰሪ ድርጅቶቹ በኩል ስምምነቱን የፈረሙት የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ክብሩ ፎንጃ እና የንብ ኢንሹራንስ ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኃ/ማርያም አሰፋ ሲሆኑ፤ በተቋራጩ በኩል በኢትዮጵያ የድርጅቱ ተወካይ ሚ/ር ዛሆ ሳንባሆ ናቸው፡፡
የቻይናው “ሬይል ዌይ ነምበር ስሪ” ኩባንያ የዋና መ/ቤቱን ሕንፃ መሠረት አራት ፎቆች የሚያወጣ ሲሆን የሕንፃውን ቀሪ ፎቆች ሌላ ኮንትራክተር እንደሚሠራ ታውቋል፡፡ የሕንፃው ግንባታ በቅርቡ እንደሚጀመር የተገለፀ ሲሆን፣ ለባንኩና ለኢንሹራንስ ሠራተኞች ለቢሮና ለባንክ አገልግሎት የሚውሉ ክፍሎች እንደሚኖሩት ታውቋል፡፡
ሕንፃው ዘመናዊ የደህንነት ጥበቃ መሳሪያዎች የሚገጠሙለት ሲሆን ለደንበኞች ምቹና ቀልጣፋ አገልገሎት ለመስጠት ከወለል በታች ባለ 4 ፎቅ የመኪና ማቆሚያ እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡
ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ አ.ማ ከተመሠረተ 14 ዓመት ሲሆነው ከ300ሺህ በላይ የአክሲዮን አባላትና ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ የተከፈለ ካፒታል እንዳለው ታውቋል፡

Published in ዜና

“አዳራሽ መፍቀድ ያለበት ባለቤቱ እንጂ መስተዳድሩ አይደለም”
ሰማያዊ ፓርቲ ነገ መብራት ሀይል አዳራሽ ሊያካሂድ የነበረውን ህዝባዊ ስብሰባ በፅህፈት ቤቱ ለማድረግ ወሠነ፡፡ ፓርቲው በአዳራሹ ህዝባዊ ስብሰባ እንዳላካሂድ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስብሰባና ሠላማዊ ሠልፍ ማሳወቂያ ክፍል እንቅፋት ሆኖብኛል ብሏል፡፡
የመስተዳድሩ የስብሰባና ሰላማዊ ሰልፍ ማሳወቂያ ክፍል ሀላፊ አቶ ማርቆስ ብዙነህ በበኩላቸው፤ የመሰብሰቢያ አዳራሽ የመፍቀድ መብት የባለ አዳራሹ እንጂ የመስተዳድሩ አይደለም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ፓርቲው “የግጭት አፈታት በኢትዮጵያ” በሚል ርዕሰ-ጉዳይ ላይ የመነሻ ሀሳብ እንዲያቀርቡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሳይንስ ፋካልቲ የሳይንስና ቴክኖሎጂ መምህር የሆኑትን ዶ/ር በቃሉ አጥናፉን መጋበዙን ገልፆ፣ አዳራሽ ለመከራየት ሲሄዱ ከአዲስ አበባ አስተዳደር ለስብሰባ ያስፈቀዳችሁበትን ደብዳቤ ካላመጣችሁ አናከራይም መባላቸውን የፓርቲው ፕሬዚዳንት ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ተናግረዋል፡፡ ከምኒልክ ት/ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽም ተመሳሳይ ምላሽ ማግኘታቸውን ኢ/ሩ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
“አዳራሽ ተከለከልን ብለን ፕሮግራማችንን አናስተጓጉልም” ያሉት ኢ/ር ይልቃል፤ ህዝባዊ ስብሰባውን በፓርቲው ጽ/ቤት ለማካሄድ መወሰናቸውን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ለሌሎች ፓርቲዎች የመስተዳድሩ ማሳወቂያ ክፍል ደብዳቤ ፅፎላቸው ስብሰባቸውን ማከናቸናቸውን የገለፁት የፓርቲው ፕሬዚዳንት፤ ለእኛ ጊዜ መስተዳድሩ ደብዳቤ አለመፃፉ ሆን ተብሎ የፓርቲውን እንቅስቃሴ ለመግታት የተደረገ ነው ሲሉ አማረዋል።
የመስተዳድሩ የስብስብና ሰላማዊ ሰልፍ ማሳወቂያ ክፍል ሀላፊ ግን በሰዎች አዳራሽ አያገባንም፤ ለአዳራሽ የከፈላችሁበትን ደረሰኝ አምጡ ማለታችን ትክክለኛ የአሰራር አካሄድ ነው ብለዋል፡፡
ስማቸውን መግለፅ ያልፈለጉ የመብራት ሀይል አዳራሽ የስራ ሀላፊ ግን በእስከዛሬው አሰራራቸው ከመስተዳድሩ ህጋዊ ስብሰባ ማካሄጃ ፈቃድ ሲያገኙ ብቻ አዳራሹን እንደሚያከራዩ ገልፀው፤ ሰማያዊ ፓርቲ ይህን ደብዳቤ ሊያቀርብ ባለመቻሉ አዳራሹን ለማከራየት መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡
በተያያዘ ዜና፤ ሰማያዊ ፓርቲ ነሀሴ 26 የሚያካሂደውን ሁለተኛውን ሰላማዊ ሰልፍ ለመስተዳድሩ የስብሰባና ሰላማዊ ሰልፍ ማሳወቂያ ክፍል ማሳወቂያውን ካስገባ በኋላ በምን ዙሪያ፣ የትና እነማን ሰልፉን እንደሚያካሂዱት በደብዳቤ እንዲገልፅ ተጠይቆ በደብዳቤ ምላሽ መስጠቱን ገልጿል፡፡

Published in ዜና

ሶኒ የኤሌክትሮኒክስ ኩባንያ የግማሽ ክፍለ ዘመን ጥረቴን ያንፀባርቃል ያለውንና አዲሱን “ኤክስፔሪያ ዜድ” የተሰኘ የሞባይል ምርት ወደ ኢትዮጵያ አስገብቷል፡፡ ሰሞኑን በይፋ ያስተዋወቀው ይሄው ምርት ወድቆ መከስከስ፣ ውሀ ውስጥ ገብቶ ስራ ማቆም አይነካካውም ተብሏል፡፡ አዲሱ ኤክፔሪያ ዜድ ሞባይል ዋጋው 18ሺህ ዘጠኝ መቶ ብር እንደሆነም የሶኒና የአከፋፋዩ የግሎሪየስ የስራ ሀላፊዎች ገልፀዋል፡፡ ምርቱ በአንድ ንክኪ የሚፈልጉትን ዘፈን ወደ ስፒከር የማዛወርና ከስፒከሩ ብቻ እንዲያዳምጡ የማድረግ አቅም እንዳለውም ተገልጿል፡፡ የሀምሳ አመት የስራ ዘመኑንና የቴክኖሎጂውን ምጥቀት እንደሚያሳይለት የገለፀው ሶኒ የጥገና ማዕከል ኢትዮጵያ ውስጥ ለመክፈት ዝግጅት ማጠናቀቁንም ይፋ አድርጓል፡፡
ኤክስፔሪያ ዜድ የምስል ጥራቱ ከ3D ቴሌቪዥን እኩል መሆኑን የገለፁት ሀላፊዎቹ ምርቱ ከድምፅ በተጨማሪ በንክኪ ምስልና ሌሎች አገልግሎቶችን ወደ ቴሌቪዥን የማሰራጨት አቅም እንዳለውም ተብራርቷል፡፡
ሰሞኑን በሂልተን ሆቴል በተካሄደው የምርቱ ይፋዊ ትውውቅ ስለ ሞባይሉ ማብራሪያ የሰጡት የግሎሪየት ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ነዲብ አብዱልሰመድ እንደተናገሩት በሞባይሉ ራስን ከተለያየ አቅጣጫ ፎቶ ማንሳት የሚቻልበት ፈጠራም ታክሎበታል ብለዋል፡፡ የጨረር ጉዳቱ ከሌሎች በአለም ላይ ካሉ ሞባይሎች በጣም ያነሰ ነው የተባለለት አዲሱ “ኤክስፔሪያ ዜድ” የኔትወርክ ችግርን ለመቅረፍ ከሁለት ጂ በላይ ይዘት እንዳለው የተገለፀ ሲሆን ባለ አምስት ኢንች ሙሉ እውነታን ያሳያልም ተብሏል፡፡ የባትሪ አቅሙን በተመለከተ ከመደበኛዎቹ ባትሪዎች በአራት እጥፍ የላቀ አገልግሎት እንዳለውና ይህም ከሌሎች ሞባይሎች ተመራጭ እንደሚያደርገው ተጠቁሟል፡፡ አዲሱን ኤክፔሪያ ዜድ ከ30 አመታት በላይ የኩባንያውን ምርቶች እያስመጣ ሲያከፋፍል የኖረው ግሎሪየት እያስመጣ ለገበያ ያቀርበዋል ሲሉ ሀላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡

Published in ዜና

በ14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና መሀመድ አማን፤ የ800 ሜትር ውድድሩን በአስደናቂ የአጨራረስ ብቃት አጠናቆ የወርቅ ሜዳልያውን ከወሰደ በኋላ፣ መደበኛው ጋዜጣዊ መግለጫ የሚሰጥበትን አዳራሽ ያጣበብነው አምስት የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች እና የብሄራዊ ቡድኑ ሃኪም ዶክተር አያሌው ነበርን፡፡ ውድድሩ ተጠናቅቆ ከምሽቱ ለአምስት ሰዓት ምናምን ጉዳይ ላይ ነው፡፡ በመሃመድ ታሪካዊ ድል ደስታችን ልክ አልነበረውም፡፡

በፕሬስ ኮንፍረንሱ አዳራሽ የተገኘነው ከየትኛውም አገር ጋዜጠኞች ቀድመን ነበር፡፡ መሃመድ አማን በ800 ሜትር ያስመዘገበው የወርቅ ሜዳልያ፣ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፈርቀዳጅ ታሪክ መሆኑን፤ በሻምፒዮናው ታሪክ በ20 ዓመቱ የርቀቱን የወርቅ ሜዳልያ ለመውሰድ የበቃ ድንቅ አትሌት እንደሆነ ጋዜጠኞች ስንነጋገር፣ ዶክተር አያሌው መሃከል ገቡና፣ መሃመድ ለ800 ሜትር እና ለአጭር ርቀት ውድድር የተፈጠረ ምርጥ አትሌት መሆኑን በመጠቆም፣ በስፖርቱ ውጤታማ ለመሆን ባለው የስራ ፍቅርና ትጋት እንደሚያደንቁት ገለፁልን ፡፡ ውይይታችን በስፍራው የነበሩ የሌላ አገር ጋዜጠኞች እና የስፖርት ባለሙያዎችን ትኩረትም ስቦ ነበር፡፡
በፕሬስ ኮንፍረንሱ አዳራሽ ከመሃመድ አማን በፊት መግለጫ የሚሰጡ የሌላ ውድድር አሸናፊዎች ነበሩ፡፡ የዲስከስ ውርወራ እና የሄፕታትሎን ተወዳዳሪ የነበሩ ናቸው፡፡

የሁለቱ ስፖርቶች አሸናፊዎች መግለጫዎች ሲሰጡ ኢትዮጵያውያኑ ባይተዋር ነበርን ማለት ይቻላል፡፡ ለነገሩ በረጅም ርቀት እንጂ በ800 ሜትር ኢትዮጵያዊ አትሌት አሸንፎ ለጋዜጣዊ መግለጫ እንበቃለን ብለን አስበንም አልመንም አናውቅም፡፡ የወንዶች ዲስከስ ውርወራ አሸናፊዎች እና የሴቶች ሄፕታተሎን ውድድር ሜዳልያ ተሸላሚዎች መግለጫ ከተጠናቀቀ በኋላ፣ ተራው የእነ መሃመድ አማን ሆነ፡፡ ወደመግለጫው የገቡት የወርቅ ሜዳልያውን የወሰደው መሃመድ አማን፤ የብር እና የነሐስ ሜዳልያውን የወሰዱት የአሜሪካ አትሌቶች ነበሩ፡፡ መሃመድ አማን የወርቅ ሜዳልያውን ያስመዘገበው የሉዝንስኪ ስታድዬም በምርኩዝ ዝላይ ተወዳዳዳሪዋ ራሽያዊት ዬለና ኢዝንባዬቫ ምክንያት ጥቅጥቅ ብሎ በሞላበት ወቅት ነበር፡፡

መሃመድ አማን በ800 ሜትር ያሸነፈው በጣም ጠንካራ አትሌቶች በተሳተፉበት የ800 ሜትር የፍፃሜ ውድድር ሲሆን ርቀቱን የሸፈነበት 1ደቂቃ ከ43.31 ሰኮንዶች የውድድር ዘመኑ ፈጣን ሰዓት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ መሃመድ አማን በ5ሺ፤በ10ሺ እና በማራቶን ውድድሮች ስኬታማ አትሌቶች ከበዙባት ኢትዮጵያ መውጣቱ እያነጋገረ ሲሆን ከአጭር ርቀት ሯጭነት ወደ መካከለኛ ርቀት ምርጥ አትሌትነት መሻገሩም ያልተጠበቀ ነው ተብሏል፡፡
ከሁሉ የሚገርመው ደግሞ መሃመድ አማን መግለጫውን የሰጠው በእንግሊዘኛ መሆኑ ነው፡፡ ይሄም ሌላ ያልተጠበቀ ነገር ሆኗል፡፡ እስካሁን ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች በአስተርጓሚ ነበር ጋዜጣዊ መግለጫ የሚሰጡት፡፡ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታውን ፊልሞች በመመልከት እና በማንበብ ነው ያዳበረው፡፡ ለመሃመድ የቀረበለት የመጀመርያው ጥያቄ ከመግለጫው መሪ የአይኤኤኤፍ ጋዜጠኛ ነበር፡፡
“መሃመድ ውድድሩ አስቸጋሪ ነበር፤ በሩጫው መሃል ወደ ኋላ ቀርተህ ከዚያ በኋላ ነው አፈትልከህ የወጣኸው፡፡ ስትራቴጂው ምን ነበር?” ሲል ጠየቀው፡፡
“የፍፃሜ ውድድር ነው፡፡ ስለዚህም ለማሸነፍ የተከተልኩት ስትራቴጂ ተገቢ ነው፡፡ በፍፃሜ ውድድር የሚሳተፉት ሁሉም አትሌቶች ምርጥ ብቃት እንዳላቸውና የማሸነፍ እድል እንደሚኖራቸው ግምቱ ነበረኝ፡፡ እስከመጨረሻዎቹ ሜትሮች ሁኔታውን እያጠናሁ በትዕግስት ተጠባብቄያለሁ፡፡ ከዚያም በአስፈላጊው ጊዜ አፈትልኬ ወጥቻለሁ፡፡›› በማለት መሃመድ ምላሹን ሰጥቷል፡፡
ቀጣዩ ጥያቄ ከፕሬስ ኮንፍረንሱ የመድረክ መሪ የቀረበ ሲሆን ያሸንፋል የሚል ግምት ለተሰጠው አሜሪካዊው ኒክ ሳይመንድስ እና ለነሐስ ሜዳልያው ባለድል የጅቡቲ አትሌት ነበር፡፡ “ኒክ ሳይመንድስ” በብር ሜዳልያው መወሰንህ ምን ስሜት ፈጠረብህ?” ተብሎ ለተጠየቀው ሲመልስ፤
‹‹በብር ሜዳልያው በጣም ደስተኛ ነኝ፤ ውድድሩ ሜትር እስኪቀረው ቀጣዩ የዓለም ሻምፒዮን መሆኔን እያሰብኩ ነበር፡፡ ግን አልሆነም፡፡ ባገኘሁት የብር ሜዳሊያ ብዙም አልተከፋሁም›› ያለ ሲሆን የነሐስ ሜዳልያ ባለቤቱ ጅቡቲያዊ በበኩሉ፤ ‹‹ደስተኛ ነኝ፤ ለአገሬ የተገኘ ብቸኛ እና የመጀመርያው ሜዳልያ ነው፡፡ ውጤቱ በጠንካራ ፉክክር የተገኘ በመሆኑም አኩርቶኛል›› በማለት መልሷል፡፡
ለመሃመድ አማን “በአገርህ ለወርቅ ሜዳልያ መጠበቅህ የፈጠረብህ ጫና ነበር ወይ” የሚል ጥያቄ ከኢንተር ስፖርት ዋና አዘጋጅ እና የአትሌቲክስ ዘጋቢ ብዙአየሁ ዋጋው ቀርቦለት ነበር፡፡
‹‹ኢትዮጵያ በረጅም ርቀት እና በማራቶን ውድድሮች ውጤታማ በሆኑ በርካታ አትሌቶቿ ትታወቅ ነበር፡፡ እኔ በአጭር ርቀት ውጤታማ በመሆኔ ብዙ ጫና አልነበረብኝም፡፡ እንዴት እንደሆነ አላውቀውም፡፡ ከፍተኛ በራስ የመተማመን ስሜት አለኝ፡፡ አራት የዳይመንድ ሊግ ውድድሮችን ማሸነፍ መቻሌ በጣም ልበ ሙሉ አድርጎኛል፡፡ የዓለም ሻምፒዮና ጠንካራ ፉክክር ያለበት ነው፡፡ በጥንቃቄ መሮጥ ያስፈልግ ነበር፡፡
ስለውድድሩ ላለመጨነቅ ስል ብዙ ሃሳብ ውስጥ አልገባሁም፡፡ ለጥ ብዬ እንቅልፌን ተኛሁ፡፡ አሰልጣኜ ስልክ ደውሎ ምን እየሰራህ ነው አለኝ፡፡ ስለ ውድድሩ ከማሰብ ጥሩ እረፍት እንደሚያስፈልገኝ አምኜበት መተኛቴን ነገርኩት” በማለት ምላሹን ሰጥቷል፡፡
የኢቴቪ ስፖርት ጋዜጠኛ እና የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዝዳንት ዮናስ ተሾመ በበኩሉ፤ “ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ አዲስ ታሪክ ሰርተሃል፡፡ በአጭር ርቀት በአለም ሻምፒዮና የተመዘገበ ብቸኛ ድል ነው፡፡ ምን ተሰማህ?” የሚል ጥያቄ አቅርቦለታል፤ ለአትሌቱ፡፡
መሃመድ ሲመልስም፤ ‹‹ምንም የማይቻል ነገር የለም፡፡ ድል እንደማደርግ እምነት ነበረኝ፡፡ ያስመዘገብኩት ውጤት ትልቅ ታሪክ ነው፡፡ ለዚህ ስኬት የመጀመርያው በመሆኔም በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ልምምዴን የምሰራው በኢትዮጵያ ነው፡፡ በእንጦጦ፣ በሰንዳፋና በአዲስ አበባ ዙርያ፡፡ በአዲስ አበባ ከሚገኙ በርካታ የብሄራዊ ቡድን አትሌቶች ጋር ነው የምሰራው፤ አሰልጣኜም ኢትዮጵያዊ ንጉሴ ጌቻሞ ነው፡፡ ›› በማለት አስረድቷል፡፡
እኔ ደግሞ እንዲህ ስል ጠየቅሁት፤ “በ800 ሜትር የዓለም ሪከርድ የያዘው፤ የዓለምና የኦሎምፒክ ሻምፒዮን የሆነው ኬንያዊው ዴቪድ ሩዲሻ ቢኖር የወርቅ ሜዳልያው እድል የጠበበ ይሆን ነበር ብለህ አላሰብክም?”
‹‹በመጀመርያ እኔ ልምምድ ስሰራ የቆየሁት ለዴቪድ ሩዲሻ ብቻ አልነበረም፤ሩዲሻ ባለመኖሩ አዝኛለሁ፡፡ ጉዳት ለብዙ አትሌቶች ፈተና እየሆነ ነው፡፡ እሱ ባይኖር እንኳን ለፍፃሜ የደረሱት ሌሎቹ ሰባት አትሌቶች እጅግ ጠንካሮች ነበሩ፡፡ እነሱን በማሸነፌ ውጤቴን አስደሳች አድርጎታል፡፡› ሲል መለሰልኝ፡፡
በመጨረሻም ወደ አገሩ ሲመለስ ደስታውን እንዴት እንደሚያከብር ነበር የተጠየቀው፡፡ አማን ወደ ትውልድ ቀዬው አሰላ ለመሄድ የሚፈልገው በመስከረም ወር ዋዜማ በብራሰልስ ከሚያደርገው የዳይመንድ ሊግ ውድድር በኋላ ነው፡፡ ከብራሰልስ በኋላ በቀጥታ ወደ እናቱ ቤት ለመሄድ እቅድ ይዟል፡፡ ቤተሰቡ በዳጉ የዓለም ሻምፒዮና እና በለንዶን ኦሎምፒክ ሲሮጥ ተመልክተውታል፡፡ በሁለቱም ውድድሮች እንዲያሸንፍ ጠብቀው አልተሳካለትም፡፡ አሁን ግን የልባቸውን አድርሶላቸዋል፡፡ የቤተሰቡን ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያዊያንን፡፡ ከብራሰልስ መልስ የዓለም ሻምፒዮና ድሉን ከወላጆቹ እና ከመላው ቤተሰቡ ጋር በፌሽታ እንደሚያከብር አማን በፈገግታ ተሞልቶ ገልፆልናል፡፡ አንድ ፌሽታ ሳይሆን ሺ ፌሽታ ይገባዋል፡፡

Page 7 of 17