“የኢትዮጵያ ታሪክ ቀደምትነት ከብዙ አገሮች በፊት የታወቀና ከፍ ያለ ቢሆንም ዕውቀትን ከትውልድ ወደ ትውልድ ማስተላለፊያ በየዘርፉ የተዘጋጁ መፃሕፍት አለመኖሩን ማስተዋሌ ገንዘብና ባንክ፤ አገልግሎትና ጥቅሙ” በሚል ርዕስ ያሳተምኩትን መጽሐፍ እንዳዘጋጅ አነሳስቶኛል ይላሉ - ያሉት ደራሲ በላይ ግደይ በመፅሃፋቸው መግቢያ፡፡ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በ40ኛው ዘመነ መንግሥት (በ1963 ዓ.ም መሆኑ ነው) የታተመው የበላይ ግደይ መጽሐፍ፤ በገንዘብና ባንክ ዙሪያ በርካታ መጃዎችን አስፍሯል፡፡
መጽሐፉ ከታተመ 38 ዓመታት ያስቆጠረ ቢሆንም ዛሬም ቢሆን ሊያነጋግሩ የሚችሉና ለጥናትና ምርምር የሚጋብዙ ሐሳቦችንም መያዙ እኔንም ለዳሰሳ እንድመርጠው አነሳስቶኛል። አገራችን ኢትዮጵያ ገንዘብን የሚያስተድድር ባንክ ቤት በማቋቋም ከዓለም የመጀመርያዋ አገር ስለመሆኗ የሚያረጋግጡ መረጃዎች አሉ የሚል መጽሐፍ ትኩረት መሳቡ አይቀርም፡፡ ለዚህ ነው የመጽሐፉ ሐሳብ ዛሬም ቢሆን ለምርምርና ጥናት ያነሳሳል ያልኩት፡፡ ደራሲ በላይ ግደይ “አክሱም በሥልጣኔ በጣም የተራመደች ስለነበረች ገንዘብ መሥራት ብቻ ሳይሆን ሰፊ ንግድና መገናኛ ስለነበራት የባንክም ድርጅት እንደነበራት መገመት ይቻላል” ቢሉም ስለ ባንክ አመሠራረት ታሪክ ማጣቀሻዎችን ያቀረቡት ግን ከአገር ውስጥ ሳይሆን ከውጭ ነው፡፡
የጣሊያኖቹ ጠረጴዛ
ባንክ የሚለው ቃል “ባንኮ” ከሚለው የጣሊያንኛ ቋንቋ ተወስዶ ነው፤ በብዙ የዓለም አገራት ገንዘብን ከመቆጣጠርና ማስተዳደር ጋር በተያያዘ አልግሎት ለሚሰጡ ተቋማት መጠሪያ ሊሆን የቻለው፡፡ የበላይ ግደይ መጽሐፍ “ባንኮ” የሚለው የጣሊያንኛ ቃል ትርጉም ወደ አማርኛ ሲመለስ ጠረጴዛ ማለት ነው ይልና የጣሊያን ነጋዴዎች ገንዘባቸውን ጠረጴዛዎች ውስጥ ማስቀመጣቸው ለባንክ ቤት ስያሜ መነሻ መሆኑን ይገልፃል፡፡ እንግሊዞች ዕዳውን መክፈል ያልቻለን ነጋዴ “ባንክራፕት” ብለው የሚጠሩት ከጣሊያውያን ልማድ ጋር ተያይዞ የመጣ መሆኑን ሲያመለክትም “በዚያን ጊዜም ከነጋዴዎቹ መካከል አንዱ በስምምነቱ መሠረት ዕዳውን ለመክፈል ያልቻለ እንደሆነ ጠረጴዛው (ባንኮው) ይሰበርበትና እሱም እንደከሰረ ተቆጥሮ ከሥፍራው ይነሳ ነበር፡፡” ይላል፡፡
ለገንዘብ መፈጠር
ምክንያት የሆኑት ማዕድናት
በግብይት ታሪክ ውስጥ ዕቃን በዕቃ መለዋወጥ በሁሉም አገራት የታየ ክስተት ነበር የሚለው “ገንዘብና ባንክ አገልግሎትና ጥቅሙ” መጽሐፍ፤ ከብቶች በግሪክ፤ በጐች በጣሊያን፣ ሩዝ በጃፓን፣ ሻይ ቅጠል በቻይና፣ በኢትዮጵያና በጐረቤት አገራቷ ደግሞ አሞሌ ጨው፣ ቁርጥራጭ ጨርቆች፣ ልዩ ልዩ እህሎች…ለዕቃ በዕቃ መገበያያነት ማገልገላቸው ያመለክትና በዘርፉ ከነበሩት ችግሮች አንዱ ስንዴ ተሸክሞ የሄደ ገብስ ተሸክሞ መመለሱ የፈጠረው ድካም መፍትሔ እንዲዘየድለት መነሻ ሆኗል ይላል። ለዕቃ በዕቃ መገበያያነት መዳብ፣ ብረትና ወርቅ የመሳሰሉት ቁርጥራጭ ማዕድናትን መጠቀም መጀመሩ ለገንዘብ መፈጠር ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ በዚህም ሸክምና ድካምን የሚያስቀር ነገር ተገኘ፡፡
የባንክ ኖት አፈጣጠር
መዳብ፣ ብርና ወርቅ የመሳሰሉት ማዕድናት ለመገበያያ ተመራጭ ከሆኑ በኋላ ልዩ ጥበቃና ክብር የሚሰጣቸው በዛ፡፡ በብርና ወርቅ የተለያዩ ጌጣጌጦችን በመስራት የሚታወቁ አንጥረኞች ሀብታቸውን የሚያስቀምጡበት ምቹ ስፍራ ስለነበራቸው ሌሎችም እየመጡ ብርና ወርቃቸውን በአደራ ማስቀመጥ ጀመሩ፡፡
ለተቀበሉት የአደራ ዕቃ የማረጋገጫ ሰነድ እየፈረሙ ይሰጡ ነበር፡፡ ለሚሰጡት አገልግሎት መጠነኛ ክፍያ መቀበል ጀመሩ፡፡ ወደ በኋላ ላስቀመጡበት ማስከፈሉን ትተው ተቀማጩን ሀብት ለሌሎች በማበደር ከሚገኘው ወለድ ለአስቀማጮችም ተጨማሪ ገንዘብ መስጠት ጀመሩ፡፡ በጣሊያኖቹ ጠረጴዛ የተጀመረው የባንክ አሰራር በዚህ መልኩ ወደ ባንክ ኖት አድጐ አሰራሩ ተመራጭና ተጠቃሚውም የበዛ ሆነ፡፡
የንስሐ አባቶችና ባንክ
በክርስትና ሃይማኖት ቀሳውስቱ ለምዕመኖቻቸው በቤተ ክርስቲያናት ከሚሰጡት አገልግሎት ውጭ በንስሐ አባትነት እየተመረጡ የብዙ ሰዎችን የግል ሚስጥርና ችግር ሰምተው ምክር ይሰጣሉ፡፡ ውድ ሊባሉ የሚችሉ ሃብትና ሰነዶችን በአደራ ያስቀምጣሉ፡፡ ለምሳሌ አንድ ባለሀብት ያፈራው ንብረት እነማን እንዴትና በምን መልኩ መውረስ እንዳለባቸው በሕይወት እያለ በኑዛዜ የሚያስቀምጠው ሰነድ በንስሐ አባት (በቄስ) ዘንድ የማኖር ልማድ ከጥንት እስከ አሁን ዘመን ሲሰራበት ይታያል፡፡ ባንክ ቤቶች በየአገሩ ተቋቁመው አዳዲስ አገልግሎች ሲፈጠሩ ከተገኙት ጥቅሞች አንዱ የግለሰቦችን ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ውድ ጌጣጌጦች፣ ሰነዶችና ሚስጢራዊ ጉዳዮችን ማስቀመጫ ግለሰቡ እራሱ የሚከፍተውና የሚዘጋው ልዩ ሳጥን ማቅረባቸው ነው፡፡
ቼክን የተካው ካርድ
የባንክ ቤቶች መቋቋም በገንዘብ አገልግሎትና አጠቃቀም ላይ በርካታ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ማድረጉ በተለያዩ ማስረጃዎች ያስረዳው የበላይ ግደይ “ገንዘብና ባንክ” መጽሐፍ፤ “ቼክና ጥቅሙ” በሚለው ምዕራፍ “ቼክ እያደረ ገንዘብን ሳይወርሰው አይቀርም፡፡ አሁንም ዓለም ዋና የመገበያያ ዘዴ አድርጐ የያዘው ቼክን ነው” ይልና ቼክ በተለያዩ አገራት ሥራን እንዴት ባለ ሁኔታ እያቀላጠፈ እንደሆነ ሲያመለክትም “አንድ ሰው 750 ብር በኪሱ ተሸክሞ ሄዶ ቆጥሮ ከመስጠትና፤ የቼክ ወረቀት ይዞ ሄዶ ጽፎ ከመስጠት የትኛው ይቀለው ይመስላችኋል?” ብሎ ይጠይቃል፡፡ ደራሲ በላይ ግደይ መጽሐፋቸውን ባሳተሙበት ዘመን ላይ ሆነው ቼክ እያደር ገንዘብን ሳይተካው አይቀርም ብለው የነበረ ቢሆንም አሁን ገንዘብን እየተካ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘው “ካርድ” የቼክ አሰራርን ኋላቀር እያደረገው ነው፡፡
አነጋጋሪው ርዕሰ ጉዳይ
ደራሲ በላይ ግደይ ገንዘብና ባንክን ርዕስ ያደረገ መጽሐፍ ሲያዘጋጁ፤ ስለ ባንክ አመሰራረት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጽፎ የሚገኘውን ታሪክ በማሳያነት ያቅርቡ እንጂ “ኢትዮጵያ በአክሱም ዘመነ መንግሥት የራሷን ገንዘብ ሠርታ ለአገልግሎት አውላ ከነበር ገንዘቧን የምታስተዳድርበት ባንክ ቤቶች እንደነበሯት መገመት ይቻላል” በሚል ያቀረቡት ሃሳብ እውነትነት እንዳለው አንዱ ማሳያ በመጽሐፉ የቀረበው የባንክ ስያሜና አመሠራረት ታሪክ ነው፡፡ የጣሊያኖቹ ጠረጴዛ (ባንኮ) ከገንዘብ ማስቀመጫነት ጋር በተያያዘ ለባንክ ቤቶች መፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡ ለብዙ መቶ ዓመታት የተለያዩ ገንዘቦችን ሰርተው ለመገበያያነት አውለው የነበሩት አክሱማዊያን ገንዘባቸውን የሚያስተድድርላቸውና የሚያስቀምጡበትን ተቋም ምን ብለው ይጠሩት ነበር? የሚለው ጥያቄ አጓጊና አነጋጋሪ ነው፡፡
ሐምሌ 6 ቀን 2005 ዓ.ም በታተመው አዲስ አድማስ ጋዜጣ “ታሪካዊቷ የትግራይ ምድር” በሚል ርዕስ (ገ.ኃ) ባቀረቡት ጽሑፍ፤ በጥንቱ የሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ግብፅ በኢትዮጵያዊያን ትተዳደር እንደነበር፤ ግብፃዊያን ያላቸው ድንቅ ሀብት ምንጭ ኢትዮጵያ፣ መሆኗን፤ ግብጽ ከኢትዮጵያዊያን ያገኘችውን ጥበብና ዕውቀት ለሮምና ለግሪክ አሳልፋ እንደሰጠች በመረጃ አስደግፈው አስነብበዋል፡፡ ይህንን መረጃ ደራሲ በላይ ግደይ በገንዘብና ባንክ መጽሐፋቸው ካነሱት መላ ምታዊ ጥያቄ ጋር አጣምረን ብንመለከተው ተጨማሪ ጥያቄዎች እንዲነሱ ይጋብዛል፡፡ ምላሹ ጥናትና ምርምር የሚጠይቅ ቢሆንም የአክሱማዊያኑ ገንዘብ ከጣሊያኖቹ “ጠረጴዛ” ጋር ያላቸው ግንኙነት ምንድነው? የሚለው ከሚነሱት ጥያቄዎች አንዱ ይሆናል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን እንዳልተጫረ ክብሪት የታመቀ ኃይልና ብርሃን ያለው የሚመስለው የዚህች አገር ጥንታዊ ታሪክ መቼ ይሆን ግልጽ ሆኖ አገርና ሕዝቡ ተጠቃሚ የሚሆንበትም ያሰኛል፡፡

Saturday, 03 August 2013 10:39

የትግራይ ጉዞ ማስታወሻ

ተናጋሪዋ ምድር

“ጋዜጠኝነት የተጀመረው አክሱም ውስጥ ነው”

የዛሬው ጉብኝታችን የሚጀምረው ከሳባ ቤተመንግሥት ነው። ከአክሱም ከተማ ምዕራባዊ አቅጣጫ፣ ትንሽ ወጣ ብሎ የሚገኘው የሳባ ቤተመንግሥት ልዩ ልዩ አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ 42 ክፍሎች አሉት፤ ሌሎች አራት አብያተ መንግሥታትም አክሱም ውስጥ ተቀብረው እንደሚገኙ ተረድተናል፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊት በአገራችን ያን የመሰለ ህንጻ ይገነባ ነበር ብሎ ለማስረዳት ይከብዳል፤ ግን እውነት ነው፡፡ ራሱ ህንጻው ዛሬም በእማኝነት እንደቆመ ይገኛል - ቆሞ የሚገኘው ሙሉ ለሙሉ አለመሆኑን ግን አንዘንጋ፤ በቁፋሮ የተገኘ ነውና!
ከሳባ ቤተመንግሥት ፊት ለፊት የቆሙ፣ ያዘነበሉና የወደቁ በርካታ ሃውልቶች ይገኛሉ። ቦታውም የነጋዴዎችና የዕደ ጥበብ ባለሙያዎች መቃብር የነበረ መሆኑን የዘላቁ ቱሪዝም ልማት አስተባባሪ አቶ ቴዎድሮስ አብርሃም አስረድተውናል።
በንግሥተ ሣባ ቤተመንግሥት ውበትና በሥራው ውስብስብነት እየተደነቅን ወደ አክሱም ሰሜናዊ ምሥራቅ አቅጣጫ ተጓዝን፤ ትግራይ ውስጥ በጥንቃቄ መጓዝ ብቻ ያስፈልጋል፡፡ ጥንቃቄው ደግሞ ዕርባና የሌለው የሚመስል ድንጋይ፣ ውሃ፣ ወይም ጉብታ በአስደናቂ ታሪክ የተዋበ ሊሆን ስለሚችል ሳናየው እንዳያመልጠን ነው፡፡
አሁን ቅድመ ልደተ ክርስቶስ የተሠራውንና በሃገራችን የመጀመሪያ እንደሆነ የሚነገርለትን ማይሹምን እየጐበኘን ነው፤ “ማይሹም” ማለት “የሹም ውሃ” ማለት መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ እንዲያውም “የአክሱም ሥያሜ የተገኘው ከዚሁ ነው” የሚሉም አሉ፤ ምክንያታቸው ደግሞ በአገውኛ ቋንቋ “አክ” ማለት “ውሃ” ማለት ሲሆን “ሱም” ደግሞ “ሹም ማለት ነው” የሚል ነው፡፡ “አክ” እና “ሱም” በአንድ ላይ “አክሱም” ይሆናል ማለት ነው፡፡
ለማንኛውም ግድቡ የንግሥቲቱ መዋኛ እንደነበር፣ አሁንም ለአካባቢው ነዋሪዎች ልዩ ልዩ አገልግሎት እንደሚሰጥ አስጐብኚያችን ነግረውናል፡፡ ግድቦቹ ሁለት ናቸው፤ የህጻናትና የአዋቂዎች መዋኛ፡፡ ግድቡ የመጀመሪያ መሆኑ ብቻ ሳይሆን የሚያስገርመው በርካታ አብያተ መንግሥትና አብያተ እምነት፣ እንዲሁም መኖሪያ ቤቶችና መቃብር ቤቶች ተቀብረው ሲገኙ ግድቡ ግን ከሶስት ሺህ ዓመታት በላይ በደለል ሳይሞላ እስካሁን መገኘቱ ነው፡፡
ከግድቡ ከፍ ብሎ ውሃ ከቦረቦረው የመሬት አካል አንድ የህንጻ ግድግዳ ይታያል፤ “እናንተ ቆፍራችሁ ባታወጡኝም በወራጅ ውሃ አጋዥነት እኔው እወጣና ምን እንደ ነበርኩ ለትውልዱ እመሰራክለሁ” የሚል ይመስላል፡፡ ከእሱ ፊት ለፊት ከሚገኝ የእርሻ መሬት ጫፍ ወደተቀለሰች ዛኒጋባ አስጐብኝያችን ወሰዱንና ሌላ ተአምር አየን፡፡
ከዛኒጋባዋ መሃል አንድ በሶስት ማዕዘን የተጠረበ ድንጋይ በኩራትም በትዝብትም በሚመስል አኳኋን ቆሟል፡፡ ሃውልቱን ያቆመው ኢዛና መሆኑን ራሱ ሃውልቱ ይመሰክራል፤ እንዲያውም ከቦታው ያነቃነቀው ሰው ዘሩ ሁሉ የተረገመ እንዲሆን ተጽፎበታል፡፡ በሃውልቱ ሶስቱም ማዕዘናት፤ በግዕዝ፣ በሳባ እና በግሪክ ቋንቋዎች የተጻፈ ተመሳሳይ መልእክት አለ፡፡
የሃውልቱ አጠራረብም ሆነ የተጻፈበት ቁም ነገር ከድንጋይነት ይልቅ ብራና አስመስሎታል። የቆመውም ኢዛና ኑብይ ወርዶ የገደለውን፣ የማረከውንና በአጠቃላይም ያገኘውን ድል የሚያበስረውን የጦር ሜዳ ዘገባ ይዞ ነው፡፡ ይህንን ምሥጢር ሳይና ስሰማ ትዝ ያለኝ ስለጋዜጠኝነት አጀማመር ሲነገረን የኖረው ምን ያህል ከእውነቱ የራቀ መሆኑን ነው፡፡
ብዙ ጊዜ ሲነገር የምንሰማው “የተማርነውም” ጋዜጠኝነት የተጀመረው አውሮፓ (ሮም) ውስጥ መሆኑን ነበር፤ ግን የእኛ አባቶች ገና ብራና እንኳ መፋቅ ሳይጀምሩ የጦርነት ዘገባዎችን ድንጋይ ላይ ያሰፍሩ ነበር፡፡ በመሆኑም የአገራችን የጋዜጠኝነት ምሁራን ርቃ ከምትገኘው ሮም ይልቅ ፊታቸውን ወደ አክሱም በማዞር ጥልቅ ጥናትና ምርምር ሊይደርጉ ይገባ ይመስለኛል፡፡ ለነገሩ ፈረንጅ ካልነገረን በቀር የራሳችን ሃቅ እውነት አይመስለንም፡፡ ይህ ክፉ ልክፍት ነው፡፡ እንዲያውም “ፊደል የመጣው ከሌላ አገር ነው” እያሉ የሚከራከሩ ሰዎችም አጋጥመውኛል፡፡ ግንኮ እኒያ ህያው ድንጋዮች የሚመሰክሩት እውነት ሌላ ነው፤ ተናጋሪዋ የትግራይ ምድር “ሹክ” የምትለን ምሥጢርም በእጅጉ የሚያኮራ ነው፡፡
ኢኖ ሊትማንን የመሰሉ አለም አቀፍ ምሁራን፤ የሃውልቶቹና ጥርብ ድንጋዮቹ ምሥጢር አማልሏቸው ወደ እኛ ይጐርፋሉ፤ በተቃራኒው እኛ ደግሞ ፈረንጅ እናመልካለን ወይም መመራመር ሳንከጅል የእነሱን መጻሕፍት ለመቃረም ወደ ፈረንጅ ሰፈር እንጋልባለን፡፡ በኔ እምነት ይህ ሐፍረት ነው፡፡ ፈረንጆች ግዕዙን ተምረው በሃውልቶቻችን እና በብራና መጻሕፍት ላይ በግዕዝ ቋንቋ የተጻፉትን ምሥጢራት ሃተታ ሰርተውባቸዋል፤ እየሠሩም ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ “ጊዘር” የተባለ ጀርመናዊ ምሑር፤ ከአራት ዓመት በፊት የአጼ ገብረ መስቀልን አጽም ማግኘቱን ይፋ አድርጓል፡፡ እኛ ግን ዛሬም እጃችንን አጣጥፈን የፈረንጅ ማረጋገጫ እንሻለን፡፡
እርግጥ ነው የአፄ ካሌብና የአፄ ገብረ መስቀል መካነ መቃብር አካባቢ፣ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ የሥነ ስብእና የሥነ ምድር ምሑራን የምርምር ሙከራ እያደረጉ መሆኑን ተገንዝበናል፤ ይህ በእጅጉ ሊበረታታ የሚገባው ድንቅ ጅምር ነው፡፡
የአፄ ካሌብ መቃብር ወይም አፄ ካሌብ ለራሳቸው እንዳስገነቡት የሚነገርለትና በ6ኛው መቶ ክ.ዘመን ተሠራ የሚባለው መቃብር አሠራር ግሩም ነው፡፡ ጣራውም፣ ግድግዳውም ወለሉም ሆነ ሳጥኑ የተሠራው ከትላልቅ ጥርብ ድንጋዮች ነው፡፡ ይህን ስመለከት እኒያ ድንቅ ጥበበኛ እጆች፣ እኒያ እጅግ ጠንካራ ሰውነቶች የማውቃቸው ያህል በፊቴ ድቅን አሉና ቀናሁባቸው፤
መቃብሮቹ የተለያየ ቅርጽና መጠን አላቸው፤ አንዳንዶቹ በዋሻ አይነት ቅርጽ ተሠርተው ለቤተሰቡ ጭምር እንዲሆኑ የተገነቡ ናቸው፡፡ ሌሎች ደግሞ በመስቀል ቅርጽ ተሰርተው አራት ኪሶች አሏቸው፡፡ በአብዛኞቹ መቃብሮች ውስጥ የተገኙ ማስረጃዎች እንሚያስረዱት፤ የያኔዎቹ ወገኖቻችን ይቀበሩ የነበረው ድንጋዩን እንደ እንጨት እየጠረቡ በድንጋይ ሳጥን የመቃብር ፋካ መሥራት ነበር፡፡
የተጀመውም ያኔ ይመስለኛል፡፡
አንዱን የድንጋይ ሣጥን የጀርመን ተመራማሪዎች ለሁለት ቆርጠው ወደአገራቸው ሊወስዱት ሲሉ የአካባቢው ሕዝብ “ቅርሳችን ከቦታው ንቅንቅ አይልም” ብሎ አስቀርቶታል፡፡ ቀደም ሲል እንደጠቀስሁት ምርምሩ በሀገራችን ምሑራን መካሄድ አለበት ያልሁትም ሊከሰት የሚችለውን የዚህ ዓይነቱን ዘረፋ ለማስቀረት ስለሚረዳና ታሪካችንን ገልብጠው ለባዕድ እንዳያወርሱብን በመስጋት ጭምር ነው፡፡
ፈረንጆች እኮ እንኳን ግኡዙን ታሪካችንን እንደፈላስፋው ዘርዓያዕቆብ ያሉ ምርጥ አዕምሮዎችን ሊዘርፉን በእጅጉ ሞክረዋል፡፡ እናም “ሐይ” ባይ ያስፈልጋል፡፡ ለነገሩ እንኳን ከምድር ውስጥ ያለው ቅርሳችን ሊጠናና ሊታወቅ ቀርቶ፣ አዕላፍ ዘመናትን ተሻግሮ ዛሬም ሕያው የሆነው ትውፊታችን ገና አልተመዘገበም፡፡ የአውሮፓ በተለይ የግሪክና የሮማ፣ እንዲሁም የአፍሪካ የዕምነት ትውፊቶች በአግባቡ ተጠንተዋል፤ ተመዝግበውም ለትውልድ እየተላለፉ ናቸው፡፡ እኛ ግን ዛሬም ፈረንጅ ካልጻፈልን ጉዳዩን ከቁብ አንቆጥረውም፡፡
ለምሳሌ ከአክሱም ከተማ ወደ ሰሜን በግምት አራት ወይም አምስት ኪሎሜትር ርቀት ላይ አንድ ቀጥ ብሎ የቆመ ሹል ተራራ አለ፤ የቦታው ስም “ተመን ዘውገ (የዘንዶ ወገን)” ይባላል፡፡ አካባቢው ደግሞ “አድ ጸሐፊ (የጸሐፊ አገር)” በመባል ይታወቃል፡፡ ከዚያ ተራራ ጋር የተያያዘ አንድ ትውፊት ይነገራል፡፡
በጥንቱ ዘመን ዘንዶ ይመለክ ነበር አሉ፤ ዘንዶው በዚያ ተራራ ይኖር ነበር፤ ውሃ መጠጣት ሲያምረው ጅራቱን በተመን ዘውገ (ተራራ መሆኑን ልብ ይሏል) ያስርና ከመረብ ወንዝ ይጠጣ ነበር የሚል ትውፊት አሁንም ድረስ በሰፊው እንደሚነገር ከአካባቢው ነዋሪዎች ተረድተናል፡፡
ጉዳዩ “ራ” ከምትባለው የግብጽ የፀሐይ አምላክ ጋር፣ ወይም ከኬንያዎቹ የዝናብ አማልክት ጋር ይመሳሰላል፡፡ “ዘንዶ ወይም እባብ ዝናብንና ቀስተደመናን የመፍጠር ችሎታ ያለው ነው፤ ቆዳውን በየጊዜው በመቀያየር ስለሚኖርም ዘለዓለማዊ ነው” ተብሎ ይታመን እንደነበር “አፍሪካን ሚቲዮሎጂ” የተባለ መጽሐፍ ያስረዳል፡፡
የእኛው የዘንዶና የዕምነት ትውፊት ግን ፕሮፌሰር ስርግው ሐብለሥላሴ “የኢትዮጵያ ታሪክ” በተባለ መጽሐፋቸው፡፡ በአጭሩ ከመነካካታቸውና አቶ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ “ከጣኦት አምልኮ ወደ ክርስትና” በሚለው መጽሐፋቸው በአጭሩ ከመዳሰሳቸው በቀር ራሱን ችሎ አልተጠናም፡፡ ሕዝቡ ግን አሁንም ትውፊቱን እየተቀባበለ ለልጆቹም እየቀበለ ነው፤ ሳምንት እንገናኝ፡፡

Published in ህብረተሰብ

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

አንድ ወዳጄ በሚኒባስ ላይ አየኋት ያላት ጥቅስ ምን ትላለች መሰላችሁ… ‘ስኮፒዮ የሌለው መኪናና ታሪኩን የማያውቅ ሰው አንድ ናቸው…’ አሪፍ አይደል! ዘንድሮ ታሪክ አዋቂና ‘ትሪክ’ አዋቂ ተምታታብንሳ! የምር ግን ምን መሰላችሁ…አንዳንድ ጊዜ ታሪክ እየተባሉ የምናነባቸውና የምንሰማቸው ነገሮች…አለ አይደል… የሆነ የፍርድ ቤት የ‘ክስ መዝገቦች’ እየመሰሉን ተቸግረናል፡፡ የምር ግን ዘንድሮ ሁሉም ነገር “እነሱ ናቸው…” አይነት ‘ጦስ፣ ጥምቡሳስ’ን ወደሌላ ማስተላላፍ እየሆነ አገራችን መካሰሻ፣ መነካካሻ እየሆነች ነው፡፡ ይቺን እውነተኛ ታሪክ ስሙኝማ… በአገራችን አንድ አካባቢ የሆነ ነው አሉ፡፡ ጎረቤታሞቹ ለረጅም ጊዜ አብረው ኖረዋል፡፡ አንድ ቀን ታዲያ የአንደኛው ቤተሰብ ልጅ ህይወቱ ያልፋል፡፡ ይሄኔ ታዲያ ነገር ይመጣላችኋል፡፡ የሟች ዘመዶች ውስጥ ውስጡን የጎረቤቶቻቸውን ስም እያነሱ “እነሱ በልተዉት ነው ህይወቱ ያለፈው…” ምናምን እያሉ ወሬው ተነዛና መንደረተኛው ጆሮ ሁሉ ደረሰ፡፡

ከጥቂት ወራት በኋላ ‘በልተዉት ነው’ ከተባለው ቤተሰብ አንድ ልጅ ይቺን ዓለም ይሰናበታል፡፡ ይሄኔ ከዘመዶቹ አንዷ ምን ብለው አለቀሱ አሉ መሰላችሁ… አንድ አምላክ ነው እንጂ የሚያደላድለው እግዚአብሔር ነው እንጂ የሚያደላድለው መድኃኔዓለም ነው እንጂ የሚያደላድለው የእናተንስ እኛ የእኛን ማን ገደለው? እናላችሁ…በሆነ ባልሆነው ጣት እየተቀሳሰርንና “እነሱ ናቸው…” እየተባለ “የእናተንስ እኛ፤ የእኛን ማን ገደለው…” የምንባል ቁጥራችን እየበዛ ነው፡፡ በልጅነት ጊዜ… ኩኩ መለኮቴ እሷ በበላችው በእኔ ላከከችው… የምትባል ነገር ነበረች፡፡ ብዙ ነገሮች ‘ኩኩ መለኮቴ’ እየሆነብን ተቸግረናል፡፡ ታዲያላችሁ…ነገረ ሥራችን ሁሉ ‘ኩኩ መለኮቴ’ አይነት ሲሆን፣ “የእኔ ጥፋት ነው፣ አስተካክላለሁ…” የሚል ሲጠፋ አሁን በየቦታው እንደምናየው ወሬያችን ሁሉ ስለ ችግርና ችግር ብቻ (እንዲሀ አይነት ‘ቃላት አጣጣል’ ሲገባባኝስ’!) ብቻ ይሆናል፡፡

እናማ… ስለ ቦተሊካ ችግር… ስለአገልገሎት አሰጣጥ ችግር… ስለ መከዳዳት ችግር… ምን አለፋችሁ፣ የችግር ዝርዝራችን ከህዝብ ቁጥር ዝርዝራችን ሊስተካከል ፉክክር ላይ ያለ ይመስላል፡፡ እናማ…አብዛኛው ችግር የሚመጣው የራሳችንን ሸክም ራሳችን ከመሸከም ይልቅ ወደ ሌላው የምናስተላልፍ እየበዛን ስለሄድን አይመስላችሁም! እናላችሁ…እንዲሁ አንድ ነገር በተፈጠረ ቁጥር “እነሱ ናቸው…” ብሎ ጣት መቀሳሰር የዘመናችን ‘ሆቢ’ ነገር ሆኗል፡፡ ነገሮች ሲበላሹ፣ በቀኝ መሄድ የሚገባው ወደ ግራ ሲንጋደድ…“እነሱ ናቸው…” ባልበላው የሚላከክበት መአት ነው፡፡ የምር ግን…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… “የእኛ ጥፋት ነው…” “ችግሩን የፈጠርኩት እኔ ስለሆንኩ ይቅርታ…” ምናምን የምንባባልበት ጊዜ አልናፈቃችሁም! ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…ምንጊዜም የተቀረው ዓለም እኛን ድባቅ ለመምታት እንዳሰፈሰፈ አድርጎ የማሰብ ነገር የህይወታችን አካል ሆኗል፡፡ ስሙኝማ…ባልና ሚስት አካባቢ “የእናተንስ እኛ፤ የእኛን ማን ገደለው?” አይነት ነገር መአት ጊዜ ይከሰታል ይባላል፡፡

“መብራቱን ሳታጠፊ ተኝተሽ አምፖሉን አቃጥለሽው አረፍሽ!” ሲላት “አንተ አይደለህ እንዴ ሌሊት፣ ሌሊት አሥሬ እየተነሳህ ስታበራና ስታጠፋ የምታድረው!” ትለውና የት ይደርሳል የተባለ ትዳር በአንዲት የ‘ቻይና አምፖል’ መቃጠል ድብልቅልቁ ይወጣል፡፡ (እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ሳምንት የማይበሩ አምፖሎች አምጥቶ የበተነብን ማነው! አሀ…በአሥርና አሥራ ምናምን ብር እየተገዙ በጥቂት ቀናት ‘ኤክስፓየር’ የሚያደርጉ አምፖሎች ‘ደምፕ’ ተደርገውብን ግራ ገብቶናላ! …ለነገሩማ…አለ አይደል…ብዙ ነገር አንድ ‘ሳምንት የማይበራ አምፖል’ እየሆነብን አይደል!) እናላችሁ…“እኔ አጥፍቻለሁ…” ማለት ‘ካፒታል ፐኒሽመንት’ ምናምን አይነት ፍርድ ‘በራስ ላይ’ እንደማሳለፍ አይነት እየተቆጠረና ነገርዬው ሁሉ… “የእናተንስ እኛ፤ የእኛን ማን ገደለው?” እየሆነ መአት ቤተሰቦች ይታመሳሉ፡፡ የባልና ሚስት ነገር ካነሳን አይቀር…ስማኝማ ወዳጄ…ባሏ ማታ እቤት ሲገባ “ምን እያደረግሽ ነው?” ሲላት “ራትህ ስለቀዘቀዘ እያሞቅሁ ነው…” ስላለችው ሴት ዛሬ እናውራ እንዴ! (ለ‘አደባባይ አይበቃም’ ብዬ ነው…) ስለ ባል፣ ሚስት ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን የሆነ ቦታ ያነበብኳትን ስሙኝማ…ከጋብቻ በኋላ መኝታ ቤቱ ምን አይነት ጠረን ይኖረዋል? ለሚለው ጥያቄ የተሰጡ መልሶች ናቸው፡፡

በመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት የሽቶና የአበባ መአዛ ይኖረዋል፡፡ ከአሥራ ሁለት ወራት በኋላ የቤቢ ፓውደር፣ ክሬም፣ ዳይፐርና ቤቢ ሎሽን አይነት መአዛዎች ይኖሩታል፡፡፡ ከሰባት ዓመታት በኋላ የሚኖረው ሽታ ምን መሰላችሁ…የህመም ማስታገሻ ኪኒኖች ሽታ! የቁርጥማት…ወዘተ. ደግሞላችሁ…ደግነቱ የዲ.ኤን.ኤ. ዘመን ሆነና ነው እንጂ…“ልጁ የአንተ፣ የራስህ ነው፣” “ያኔ ለምነህ እንትን ብለህ ደግሞ የእኔ አይደለም ልትል ነው!” አይነት ‘ኩኩ መለኮቴ’ መአት ነው፡፡ “የትም እንትን ብለሽ ያመጣሽውን… አባቱን እዛው ሄደሽ ፈልጊ!” አይነት ‘አንዱ በበላው፣ በሌላው ማላከክ’ መአት ግንኙነቶችን አፍርሷል፡፡ ይቺን ስሙኝማ…ሴትዮዋ ለሆነ የሬድዮ ቶክ ሾው ስልክ ትደውልና ምን ትል መሰላችሁ… “ሦስት ልጆቼን ይዞ ባዶ ቤት ጥሎኝ ለጠፋው ባለቤቴ መልእክት እንድታስተላልፉኝ ነበር፡፡” “እሺ አድማጫችን፣ መልእከትሽ ምንድነው?” ይሏታል፡፡ ይሄኔ እሷ ሆዬ ምን ብትል ጥሩ ነው… “እባክህ ከሦስቱ ልጆች ሁለቱን መልስልኝ፣ አንደኛው ብቻ ነው የአንተ ልጅ በሉልኝ፡፡” እንዲህም አለላችሁ! እናላችሁ…ብዙ ጊዜ የሆነ ነገርን ማን እንዳበላሸው “ፀሐይ የሞቀው፣ አገር ያወቀው…” ነገር ነው፡፡ ታዲያላችሁ…ነገርዬውን ማን እንዳበላሸው እየታወቀ… “እነሱ ናቸው…” ምናምን ሲባል ስትሰሙ…አለ አይደል…መግባባት ችለን ‘የቄሳሩ ለቄሳር’ የሚሆንበት ዘመን ለምን ቀን በቀን ጭርሱን እየራቀን እንደሚሄድ ግራ አይገባችሁም! ስሙኝማ…የዚህ አገር ‘ቦተሊካ’ ትልቁ ችግራችን (አንዳንዴ “ችግራቸው…” ለማለት ዳር ዳር አይላችሁም!)…በቃ ትናንት ለነበረውም፣ አሁን ለሚፈጠረውም ችግር ሁሉ …“እነሱ ናቸው…” የሚሉት አባዜ ነው፡፡ እኔ የምለው…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…አንዳንድ ጊዜ “ምንም ነገር አለማወቅ ይሻል ይሆን!” ያሰኛል፡፡ ጭንቀት የለ…“ይቺ አገር ወዴት እየሄደች ነው?” አይነት ነገር የለ…በቃ፣ ዋናው አጀንዳ “ይሄን የቢራ ዋጋ መቼ ነው የሚያወርዱልን?” የሚል ይሆንና ቢያንስ፣ ቢያንስ ለአሞክሲሊን የምንመድበው በጀት ይቀንስልናል፡፡

እናላችሁ… ዛሬ ከሰዓት በኋላ ‘ውሀ’ አካባቢ ተሰብስባችሁ…አለ አይደል…ከመሀላችሁ …“በቀደም በአፍሪካ ዋንጫ ተካፈልን ነበር ሲሉ የሰማሁት እውነት ነው እንዴ?” ወይም “እናንተ ሙባረክን ገለበጡት አሉ…” የሚላችሁ ሰው…ምን አለፋችሁ… ‘የሸረሪት ድር ያደራበት ጭንቅሌ ይዞም ቢሆን’ ለሽ ብሎ ይተኛል፡፡ እናላችሁ…አንድ ነገር ሲፈጠር “ጠላቶቼ ናቸው እንዲህ የሚያስወሩብኝ…” “ምቀኛ ጎረቤት ጠቁሞብኝ ነው…” “የፔርሶኔሉ ጸሀፊ ስለማትወደኝ ሹክ ብላ ነው እየተባለ…” አንዱ በበላው በሌላ እየተላከከ የአገሪቱ ጣቶች በሙሉ የሚጠቁሙት ወደ ሌሎች ብቻ ሆኗል፡፡ “የእናተንስ እኛ፣ቀ የእኛን ማን ገደለው?” አይነት አባባልን ‘ታሪክ’ የሚሆንበትን ዘመን ያፍጥልንማ! ደህና ሰንብቱልኝማ!

Published in ባህል

የኔትዎርክ አለመኖር ከጉድ አወጣኝ”
ዕድሜና ጤንነት ያልበገረው የሥልጣን ፍቅር (የ89 ዓመቱ ሙጋቤ!)

የዚምቧቡዌው ፕሬዚዳንት የ89 ዓመቱ ሮበርት ሙጋቤ፤ ዛሬም ሥልጣንን የሙጥኝ ማለታቸው አይገርማችሁም? (ሥልጣን ሃሺሽ ሳይሆን አይቀርም!) እንዴ --- አገራቸው ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነፃ ከወጣች በኋላ እኮ የሥልጣኑን መንበር ለማንም አላስነኩም። እናላችሁ--- ይኸው ለ33 ዓመት ከቤተመንግስት አልወጣም ብለው አሻፈረኝ ብለዋል። (የአገር ልጅ ቅኝ ግዛት ማለት እኮ ነው!) እድሜም ሆነ ጤና ከሥልጣን አያግደኝም ብለው የተፈጠሙት ሙጋቤ፤ ባለፈው ረቡዕ ለሰባተኛ ጊዜ ለፕሬዚዳንትነት መወዳደራቸውን ሰምተናል። (ሥልጣን የምሰጠው ሞቼ ነው ቆሜ በሚል እልህ!) ባለፈው መጋቢት ወር የአገሪቱ ፕሬዚዳንት የሥልጣን ዘመን በሁለት ዙር የተገደበ ቢሆንም ህጉ ወደ ኋላ ተመልሶ ስለማይሰራ ሙጋቤን “አሁንስ በቃዎት” ለማለት አለመቻሉን ምንጮች ጠቁመዋል። እናም በዘንድሮው ምርጫ መወዳደር ብቻም ሳይሆን ምርጫውን እንዳሸነፉ ከፓርቲያቸው የወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ተፎካካሪው ፓርቲ “ሙቭመንት ፎር ዲሞክራቲክ ቼንጅ” በበኩሉ፤ ምርጫው መጭበርበሩንና ውጤቱ ፈፅሞ ተቀባይነት እንደሌለው አስታውቋል - “ትልቅ ቧልት ነው” በማለት። የምርጫ ታዛቢዎች በሰጡት አስተያየት ደግሞ አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ ዚምባቡዌያውያን እንዳይመርጡ የሙጋቤ ፓርቲ ጫና ማድረጉን ገልፀዋል። “ድሉ የእኛ ነው” ለማለት የተጣደፈው የሙጋቤ ፓርቲ፤ “ምርጫው ነፃ ፤ፍትሃዊና ተዓማኒ ነበር” ብሏል። (የልቡን ሰርቷላ!) እኔ የምለው ግን---- የዚምባቡዌ ፓርቲዎች ሌላው ቢቀር የመተካካት ስትራተጂን እንኳን ከእኛ አይማሩም እንዴ? (ከኢህአዴግ ማለቴ ነው) በነገራችሁ ላይ --- 89 የመኢአድ ፅ/ቤቶች ራሳቸው በፃፉት ደብዳቤ ተዘግተዋል የሚል ነቀፌታ የሚሰነዘርባቸው ኢንጂነር ኃይሉ፤ በቅርቡ ከፕሬዚዳንትነት ሥልጣናቸው የወረዱት በመተካካት ስትራቴጂ ነው ወይስ ደክሟቸው? (ኸረ ይበቃቸዋል!)

አንድ ጎልማሳ ባለትዳር ነው አሉ። ምሽቱን ሲጠጣ ይቆይና ወደ ቤቱ እየሄደ ሳለ ምን እንዳሳሰበው አይታወቅም የድሮ ፍቅረኛው ድንገት ትዝ አለችው። (አብሾ ይኖርበት ይሆን?) ጎልማሳው ትንሽ ያስብና ሞባይሉን ከኪሱ ውስጥ መዥረጥ አድርጎ ያወጣል - ሊደውልላት (“አደጋ አለው” ማለት ይሄኔ ነው!) ቢሞክር ቢሞክር ግን እምቢ አለው። ኔትዎርክ የለም። ተስፋ ቆርጦ ወደ ቤቱ ያመራል - ወደ ትዳሩ። ጠዋት ስካር በርዶለት ከእንቅልፉ ሲነቃ የማታው ትዝ አለው። የደወለ መስሎት ለአፍታ መደንገጡ አልቀረም። በደንብ ሲያስታውስ ግን አልደወለም። ዕድሜ ለኢትዮ- ቴሌኮም - ኔትዎርክ አልነበረም። እፎይ ያለው ይሄን ጊዜ ነው። ያን ሰሞን ለጓደኞቹ ከዚህ ሌላ ወሬ አልነበረውም “እናንተ ጉድ ሆኜላችሁ ነበር---- ኔትዎርክ አለመኖሩ እኮ ነው ያተረፈኝ” እያለ የኢትዮ - ቴሌኮምን ውለታ ሲደሰኩር ሰነበተ። (ከዚያን ጊዜ በኋላ በኔትዎርክ ተማርሮ አያውቅም!) ወዳጆቼ --- አንዳንዴ የኔትዎርክ አለመኖር ከ“አደጋ” ሊያድናችሁ ይችላልና ዝም ብላችሁ አትማረሩ ለማለት ያህል ነው። (ብትማረሩም ለውጥ የለውማ!) በነገራችሁ ላይ ይሄ ለውሃና ለመብራት አይሰራም። ለምን መሰላችሁ? እስካሁን በውሃ ወይም በመብራት አለመኖር “ከጉድ ዳንኩኝ” ያለ አልሰማንማ!
እኔ የምላችሁ ---- የኦሮምያ ውሃና ኮንስትራክሽን ፅ/ቤት ሃላፊዎች በሙስና ተጠርጥረው መያዛቸውን ተከትሎ የጠፋችው ውሃ እንደቀልድ እኮ ሳምንት አለፋት (ምን ይሆን መላው?) እናንተ “የመንግስት ሌቦች” ጉድ አፈሉ አይደለም እንዴ? የሚገርመው እኮ ምን መሰላችሁ? አንድ መ/ቤት ውስጥ በሙስና የሚጠረጠሩ ግለሰቦች አሉ ከተባለ፤ ከዋናው ሃላፊ አንስቶ እስከሹፌሩ ድረስ ያልተነካካ ማግኘት አዳጋች እየሆነ ነው ተብሏል። አሁን እኮ ተጣርቶ እስኪነገረን ድረስ የምናምነው ሰው ሁሉ ልናጣ ነው (ሁሉም “የመንግስት ሌባ ነው” አልወጣኝም!) እውነቴን ነው የምላችሁ---- ዛሬ ማታ በኢቴቪ ስለ ኪራይ ሰብሳቢዎችና ህገወጦች ለጥናት ፅሁፍነት የሚበቃ ቶፕ ጉደኛ ዲስኩር ሲደሰኩር የሰማችሁት ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊ፤ ነገ ጠዋት በፀረ ሙስና ኮሚሽን የምርመራ ቡድን ቁጥጥር ሥር ውሎ ክው ያደርገናል። (ጠላታችሁ ክው ይበልና!)
በነገራችሁ ላይ አዲሱ የጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ መንግስት በ“መንግስት ሌቦች” እና በ“ግል ሌቦች” ላይ እየወሰደ ያለው ቁርጠኛ እርምጃ ምስጋና ሊቸረው ይገባል። ራሳቸው ጠ/ሚኒስትሩም ቢሆኑ “ሙስናን የደፈሩ መሪ” ብንላቸው የሚበዛባቸው አይመስለኝም። እስቲ አስቡት--- በኢህአዴግ የሁለት አስርት ዓመታት የሥልጣን ዘመን፤ በዘንድሮ መጠን ሞሳኝ የመንግስት ባለሥልጣኖች ተይዘው ለፍርድ የቀረቡበት ጊዜ እኮ የለም። እኔ እንደውም አሁን አሁን እያሳሰበኝ የመጣው ምን መሰላችሁ? ሙሰኞችን እያደኑ መያዙ ራሱ የሙሉ ጊዜ ሥራ መሆኑ ነው። ወደፊት ግን ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ በአባላት ምልመላውም ሆነ በአሿሿሙ ላይ ልዩ ጥንቃቄ ማድረግ የሚገባው ይመስለኛል። (ሞሳኞች ከሰማይ አልወረዱማ!) እንዴ --- በሃላፊነት የተሰጣቸውን መ/ቤት ተባብረው የሚዘርፉ ሹማምንት እንዲህ ሲበዙ እኮ የፓርቲውንም ገፅታ ያበላሻሉ። በአፍሪካ “ተወዳዳሪ አይገኝለትም” የተባለ ፓርቲ፤ኪራይ ሰብሳቢነት በተጠናወታቸው የራሱ አባላት ሲሰናከል ማየት ያንገበግባል (አባል ሳይሆኑ መቆርቆር አይቻልም እንዴ!) እናላችሁ --- ኢህአዴግ ነፍሴ የአባላቱን ቁጥር ሰማይ አደርሳለሁ ብሎ በቅጡ ሳያበጥር መመልመሉ ቢቀርበት ነው የሚሻለው (ዳፋው ለእኛ ተረፈና! )
እኔ የምላችሁ ---- በአዲሱ የጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ መንግስት ያየናቸውን ሌሎች አበረታች ለውጦች መግለፅ ተገቢ አይደለም እንዴ? (ጥፋት ስናይም እኮ አንምርም!) “የምን ለውጥ - ነው ያላችሁት?” እሺ አድምጡኝና (መደማመጥ እኮ ነው የጠፋው!) የምትሉትን በሉ። አንደኛው ለውጥ በፓርላማ የታየው አዲስ መነቃቃት ነው። (አቦይ ስብሃትና አትሌት ኃይሌ መስክረውለታል!) ሌላው ለውጥ በኢቴቪ ላይ የተስተዋለው ነው - ዘገባውን ሚዛናዊ ከማድረግና የተቃዋሚዎችን እንቅስቀሴ ሽፋን ከመስጠት አንፃር ቀላል የማይባል መሻሻል አሳይቷል። (ህዝባዊነቱን በቅጡ ማሳየት ቢቀረውም) እንደቀድሞው ጊዜ በ“ሚዲያ ዳሰሳ” ላይም የግል ሚዲያውን ጋዜጠኞች ማወያየትም ጀምሯል! (ወረት እንዳይሆን እንጂ!) በሶስተኛነት የሚጠቀሰው ለውጥ ደግሞ ለስምንት ዓመታት ታግዶ የቆየው ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት መፈቀዱ ነው (ህገመንግስታዊ መብት መሆኑ ቢታወቅም!) ስለዚህ ወደ አመራሩ ከመጣ ወደ አንድ ዓመት ገደማ ሊያስቆጥር አንድ ወር ብቻ የቀረውን የጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ መንግስትን፤ “በርታ ወደፊት እንጂ ወደ ኋላ አትመልከት” ልለው እፈልጋለሁ (ህገመንግስታዊ መብቴ መሰለኝ!)
እኔ የምላችሁ ግን---- የመንግስት ሠራተኞች በግድ ኢህአዴግ ሁኑ፤ “ያለዚያ የደሞዝ እድገትም ሆነ ሹመት አታገኙም” ይባላሉ እንዴ? እርግጠኛ ነኝ --- ኢህአዴግ ምን የዋህ ቢሆን ይሄን አያደርገውም ብዬ አምናለሁ ፤ ካደረገው ግን ራሱን ለውድቀት እያዘጋጀ ነው ማለት ነው። (ደርግ በግዳጅ አባል ያደርግ ነበር ልበል) በነገራችሁ ላይ --- ኢህአዴግም ሆነ ተቃዋሚዎች ፖለቲካዊ አመለካከትን ሰው ላይ በግድ ለመጫን ሲሞክሩ --- ህገመንግስቱን እየጣሱ መሆኑን ሊያስታውሱ ይገባል። የነፃነትና የመብት አፈናም ነው። የሰብዓዊ መብት ድፍጠጣ ልትሉትም ትችላላችሁ! (ወደፊት መሄዱ ይቀራል እንጂ ወደ ኋላማ አንመለስም!)

            የተስተካከለ ቁመናውና የስፖርተኛ አቋሙ የብዙ ሴቶችን ዓይን ይስባል፡፡ ጐተራ አካባቢ በሚገኝ አንድ ጂምናዚየም ውስጥ ተቀጥሮ ደንበኞቹን ስፖርት ያሰራል፡፡ በተግባቢነቱ፣ በተጨዋችነቱና በሰው አክባሪነቱ ሁሉም ይወዱታል፡፡ ከሥራው ቦታ ሳይርቅ ጎተራ ላንቻ አካባቢ ከግለሰብ በተከራየው አንድ ክፍል ቤት ውስጥ እየኖረ ሳለ ነው ህይወቱን የሚቀይር አንድ አጋጣሚ የተፈጠረው፡፡ ያቺን ዕለት አይረሳትም፡፡ ሴትየዋ ጠና ያሉ ናቸው - ከ50 ዓመት በላይ ይሆናቸዋል፡፡ የተደላደለ ኑሮ እንዳላቸው ሁለመናቸው ይናገራል፡፡ የጂም ደንበኛ ሆነው ሲመዘገቡ ምንም የተለየ ነገር ይፈጠራል ብሎ አላሰበም፡፡ እንደ ሁልጊዜው በፈገግታና በትህትና ተቀብሎ አስተናገዳቸው፡፡
የሴትየዋ የፊት ገፅታ የዕድሜያቸውን መግፋት ቢያጋልጥም በተለያዩ ሜካፖችና ቅባቶች እንዲሁም በዘመናዊ አለባበሣቸው ወጣት ለመምሰል ጥረዋል። እንዲህ ያሉ ወይዘሮዎች በአብዛኛው አንቱ መባልን አጥብቀው እንደሚጠሉ ያውቃል። ለዚህም ነው “አንቺ” እያለ ማናገር የጀመረው። አዲሷ የጂም ተማሪ፣ ወጣቱ ላይ ዓይናቸውን ጥለዋል፡፡ ዘንካታነቱና የስፖርተኛ ቁመናው ማርኳቸዋል፡፡

የለበሰው ቲ-ሸርትና ቁምጣ በጡንቻዎቹ ተወጣጥሯል፡፡ አይናቸውን ከሱ ላይ መንቀል ተሣናቸው፡፡ በስፖርት ሰበብ መቀራረብና መነካካት መኖሩን ደግሞ ወደውታል፡፡ ከወገብሽ ጎንበስ እግርሽን ከፍ ክንድሽን ዘርጋ ከደረትሽ ገፋ እያለ ---የሚሰሩትን እንቅስቃሴ ይነግራቸዋል አንድ ሁለት አንድ ሁለት እያለ፡፡ እሳቸው ግን ብዙም አይሰሙትም፡፡ ሁለመናቸው የሚነቃቃው ቀረብ ብሎ ሲያሰራቸው ነው - ወገባቸውን ደገፍ፣ ክንዳቸውን ያዝ፣ እግራቸውን ሳብ እያደረገ ሲያንቀሳቅሳቸው አንዳች የተለየ ዓለም ውስጥ የገቡ ይመስላቸዋል፡፡ የሰራ አካላቸው ይፍታታል። ፊታቸው ይበራል፡፡ ጨዋታቸው ይደራል፡፡ ለመግባባት ጊዜ አልፈጀባቸውም፡፡ ሲውል ሲያድር መግባባታቸው እየጠነከረ፣ግንኙነታቸው የተለየ መልክ እየያዘ መጣ፡፡
ወጣቱ አሰልጣኝ የሴትየዋን ስሜት ተረድቶታል፡፡ እሳቸው በቀደዱለት ቦይ መፍሰሱን አልጠላውም - የት እንደሚደርስ ባያውቀውም፡፡ ከልጅነት ጀምሮ ከሚያውቀው የድህነት ህይወት ያላቅቀው እንደሆን ማን ያውቃል? ሴትየዋ የስፖርት ሰዓታቸውን ከቀን ወደ ምሽት ሲያዛውሩትም ለምን ብሎ አልጠየቃቸውም፡፡ ልሸኝህ የሚለው ነገር የመጣውም ይሄኔ ነው፡፡ ቤቴ ቅርብ ነው ብሎ መከራከር አልፈለገም፡፡ ወይዘሮዋ ብልሃተኛ ናቸው፡፡ መንገዱን ማርዘምያ መላ አላጡም፡፡ ይሄ ኮረኮንች ነው፣ያኛው እግረኛ ይበዛዋል እያሉ ጨለማ ጨለማውን ዙሪያ ጥምጥም ይዘውት ይሄዳሉ። እንዲያም ሆኖ መድረስ አይቀርም፡፡ “ደህና እደሪ” ብሎ ከመኪና ሲወርድ፣ ጎተት አድርገው ጉንጩን መሳም አስለምደውታል፡፡ መሳሳሙ ከጉንጭ ወደ ከንፈር ለመዝለል ጊዜ አልፈጀበትም፡፡ መሸኛኘት ብቻ ሳይሆን አብሮ ማምሸትም ተጀምሯል፡፡ እራት ግብዣው ቀልጧል፡፡ ውድ ውድ ስጦታዎች እየጎረፉለት ነው፡፡ ረብጣ ብሮች ሸጎጥ ይደረግለታል።
ወጣቱ እስራው ቦታ ድረስ ሰተት ብሎ የመጣለትን ሲሣይ በደስታና በእልልታ የማይቀበልበት ምክንያት አልታየውም፡፡ መጪውን ያሳምረው እንጂ፡፡ ሴትየዋ በጥቂት ሣምንታት እጃቸው ውስጥ የገባላቸውን ግዳይ፣እያንከበከቡ ወደ መኖርያ ቤታቸው ይወስዱ ጀመር፡፡ አብሮ መዋል አብሮ ማደር መጣ፡፡ የጎመዡበትን ዘንካታ ቁመናና የተደላደለ ሰውነት፣ እንደልባቸው አገኙት፡፡ በፈርጣማ ክንዱ አቅፎ በትኩስ የወጣትነት ትንፋሹ አሞቃቸው፡፡ እርጅና ተባርሮ ወጣትነት ዳግም ተመልሶ የመጣ መሰላቸው፡፡ ዓለማቸውን አዩ፡፡ እሱም የምኞቱን አገኘ፡፡ 300ሺህ ብር አውጥተው የገዙትን አዲስ ሞዴል ያሪስ መኪና በስሙ አዛውረው ሰጡት፡፡ ከኪራይ ቤት አውጥተው በ440ሺህ ብር ኮንዶሚኒየም ገዝተው አስገቡት፡፡ ፍቅራቸው ደራ፡፡
የሴትየዋ ባለቤት ከሁለት አመት በፊት ነው በድንገተኛ ህመም የሞቱት፡፡ ሁለት ልጆቻቸው ያሉት ደግሞ ጣሊያን ነው፡፡ እናም ምንም የሚያሳስባቸውና ነፃነታቸውን የሚጋፋ ነገር አልነበረም፡፡ ወይዘሮዋና ወጣቱ ያለገደብ ደስታቸውን አጣጣሙት፣ አንድም የቀራቸው የመዝናኛ ቦታ የለም - ሁሉንም በየተራ አዳረሱት፡፡ ወጣቱ የጂም አሰልጣኝ ሥራውን ለቆ ወይዘሮዋን መንከባከብ የሙሉ ጊዜ ሥራው አደረገው፡፡ ከእጃቸው የማይለዩት ቦርሳቸው አደረጉት፡፡ በፍቅር ከነፉለት፡፡ የወዳጅ ዘመድ ምክር የሚሰሙበት ጆሮ አልነበራቸውም፡፡ “ኧረ ተይ --- አሁን ይሄ ጎረምሳ ልጅሽ አይሆንም?” የሚሏቸውን ሁሉ ጠሏቸው፡፡ ባስ ሲልም ራቋቸው፡፡ ጓደኞቻቸውንማ ልክ ልካቸውን ይነግሯቸዋል “ምቀኝነት ነው፤ እንዲህ የሚያደርጋችሁ --- ያጣ ወሬ ነው” አፋቸውን ያሲዟቸዋል፡፡

እሱም ታዲያ ከጓደኞቹ የሚያበሽቀው አላጣም “እናትህ ከምትሆን ሴት ጋር ምን ነካህ?” ይሉታል፡፡ እሱም “ምቀኞች! እናንተ ባታገኙ ነው” ይላቸዋል፡፡ የነብርን ጭራ አይዙም ከያዙም አይለቁም እንዲሉ በሴትየዋ ዘንድ ለመወደድና ለመታመን መትጋቱን ቀጥሏል። ብዙም ሳይቆይ የወ/ሮዋን ሱፐር ማርኬት የማስተዳደር ኃላፊነት ተረከበ፡፡ “እሷ የስኬቴ ሰበብ ናት፡፡ ያልኳትን የምታደርግልኝ የጠየኳትን የምትሰጠኝ የፈለኩትን የምታሟላልኝ ዓለሜ ናት፡፡” የሚለው ወጣቱ፤ ከእኔ የሚጠበቀው እሷን መንከባከብና በፍቅር ማጥገብ ብቻ ነው” ይላል፡፡ የቀድሞ ጂም አሰሪ ዛሬ ወጣት አባወራ ሆኗል፡፡ “ሃኒ” እያለ ከሚያቆላምጣቸው ወይዘሮ ጋር በትዳር ተሳስሮ ሲኖር ሁለት ዓመት አስቆጥሯል፡፡
ዛሬ ዛሬ ሹገር ማሚዎች የልጅ ልጆቻቸው የሚሆኑ ለጋ ወጣቶችን በገንዘባቸው አጥምደው፣ የወሲብ እስረኛ የሚያደርጉበት ሁኔታ በከተማችን የተለመደ ተግባር እየሆነ መጥቷል፡፡ ሹገር ማሚዎቹ የኢኮኖሚ አቅማቸው የዳበረ፣ የፈለጉትን ለማድረግ የሚያስችል በቂ ገንዘብ ያላቸው፣ ዕድሜያቸው ከ48-65 ዓመት የሚሆናቸው ሲሆኑ ልጅና ቤት ንብረት ኖሮአቸው ትዳራቸው በሆነ ምክንያት የፈረሰ ወይም ባሎቻቸውን በሞት ያጡ፣ አንዳንድ ጊዜም በትዳር ውስጥ ሆነው ከባሎቻቸው የሚፈልጉትን የወሲብ ደስታ በተለያየ ምክንያት ማግኘት የተሳናቸው ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ሹገር ማሚዎች፤ የቡና ቤት ባለቤቶች፣ ልጆቻቸው በውጪ አገር የሚኖሩና የራሳቸው ድርጅት ያላቸው ዘናጭ ሴቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ሴቶች በአብዛኛው የሚያጠምዱት ዕድሜያቸው ከ23-30 ዓመት የሚሆናቸው ጥሩ ቁመናና ደንዳና ሰውነት ያላቸው፣ ተግባቢና ተጫዋች ወጣት ወንዶችን ነው፡፡ ወጣት ወንዶች፤ ሹገር ማሚዎችን የሚቀርቧቸው ለገንዘባቸው ብለው ነው፡፡ ይሄን ደግሞ ራሳቸው ሹገር ማሚዎቹ ቢያውቁም ሌላ አማራጭ ግን የላቸውም፡፡ በርካታ ወጣት ወንዶችም ለጊዜያዊ ችግራቸው መወጫ እነዚህን ሴቶች የሙጢኝ ብለው ሹገር ቤቢነቱን ያሣምሩታል፡፡
“የተወለድኩት ከድሃ ቤተሰብ ነው፤ትምህርቴን እንኳን በአግባቡ መማር እንዳልችል ድህነቴ ትልቅ እንቅፋት ሆኖብኛል፡፡ ከ10ኛ ክፍል ላይ የተቋረጠው ትምህርቴ እዛው ላይ እንደቆመ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ሥራ የለኝም፡፡ ህይወት ለእኔ አስቸጋሪ ነበረች፡፡ ተምሮ ሥራ ይዞ ይጦረናል ለሚሉት ደካማ ወላጆቼ፣ እኔው ራሴ ተጧሪና ሸክም መሆኔ በጣም ያበሳጨኝ ነበር፡፡ በተፈጥሮ የታደልኩት ጥሩ ቁመናና ደንዳናው ሰውነቴ ችግረኛ መሆኔን እየደበቁልኝ በምቾት የምኖር ያስመስሉኛል፡፡ ሰፈር አካባቢ ቆሞ መዋሉ ሲሰለቸኝ አካባቢያችን በሚገኝ አንድ ትልቅ የሴቶች ፀጉር ቤት አጠገብ የሞባይል ማደሻ ሱቅ ከፍቶ ከሚሰራው ጓደኛዬ ጋ እየሄድኩ መዋል ጀመርኩ፡፡ ይህም ከማሚ ጋር የምትዋወቅበትን አጋጣሚ ፈጠረልኝ፡፡

እውነት ለመናገር እኔ ስተዋወቃት በመጀመሪያ ለእንደዚህ አይነት ጉዳይ አስቤአት ወይንም እሷ አስባኛለች ብዬ አልነበረም፡፡ ፀጉሯን ለመሠራት ወደ ፀጉር ቤቱ በመጣች ጊዜ ሁሉ መኪናዋን የምታቆመው በጓደኛዬ ሞባይል ማደሻ ሱቅ በራፍ ላይ ነበር፡፡ ትውውቃችን እያደገ ሲሄድ ረዘም ላለ ጊዜ አብሮ መጫወትና መነጋገሩን ቀጠልን፡፡ ከፀጉር ቤቱ ተሰርታ ስትወጣ፤ ሻይ እንጠጣ እያለች ይዛኝ መሄድ ሁሉ ጀመረች፡፡ ጓደኛዬ ሁኔታው እንዳላማረውና ሴትየዋ ልታጠምደኝ እንደሆነ ነገረኝ፡፡ አድርጋው ነው፡፡ አብረን ቆይተን ስንለያይ እንደዘበት ጃኬት ኪሴ ውስጥ የምትሸጉጣቸው ረብጣ ብሮች ስንቱን ችግሬን እንደሸፈኑልኝ እኔ ነኝ የማውቀው፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ ቤቴን ላሳይህ ብላ ይዛኝ ሄደች፡፡ ሳር ቤት አካባቢ ያለው የሴትየዋ ቤት ዘመናዊ ቪላ ነው፡፡ ቤቱ ከባሏ ጋር ፍቺ ሲፈፅሙ የደረሳት እንደሆነ ነገረችኝ፡፡ ከባሏ ጋር የተለያየችው ስሜቷን ሊጠብቅላት ባለመቻሉ እንደሆነም አጫወተችኝ፡፡ ታዛዥ ፍቅረኛዋ ሆንኩ፡፡ የእናትና የልጅ ያህል የተራራቀውን ዕድሜያችንን ዘንግተን አብረን ማበዱን ተያያዝነው፡፡ ቤተሰቦቼን ከድህነት አወጣሁ፡፡ ያማረ ለብሼ ጥሩ መኪና ይዤ ወደአደኩበት ሰፈር ስሄድ መንደርተኛው ሁሉ ያከብረኛል፡፡ ለቤተሰቦቼ ሀብታም ሚስት ማግባቴን ነገርኳቸው እንጂ “ሚስቴን” አላሳየኋቸውም፡፡ በኋላ ላይም ከሴትየዋ ጋር የማደርገው ወሲብ አልጥምህ አለኝ፡፡ በዚህ ላይ በድህነት ዘመኔ አፈቅራት የነበረች ጓደኛ ነበረችኝ፡፡

ከሴትየዋ ጋር ከተዋወቅን ጀምሮ የራቅኋት ቢሆንም አልፎ አልፎ ማስታወሴና መናፈቄ አልቀረም፡፡ ጓደኛዬን ፈልጌ አገኘኋትና ጓደኝነታችንን ቀጠልን፡፡ አሁን ኑሮዩ የተደላደለ ሆነ፡፡ ገንዘብና ድሎትን ከማሚ፣ ፍቅርን ከጓደኛዬ ማግኘት ጀመርኩ፡፡ ይህ ሁኔታዬ ግን ብዙ አልቆየም፡፡ ማሚ ከጓደኛዬ ጋር ያለኝን ግንኙነት ደረሰችበት፡፡ ፀባችን እየከረረ ሄደ፡፡ በዚህ ጊዜ እኔ በቂ ገንዘብና ንብረት ይዤ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ሹገር ማሚዬ እንደማታስፈልገኝ እርግጠኛ ነበርኩና ሆን ብዬ ፀቡ እንዲከር አድርጌ ተለየኋት፡፡ ራቫ ፎር መኪናዋንና በርካታ መጠን ያለው ገንዘቧን ግን በእጄ ለማድረግ ችያለሁ፡፡”
በትዳር ውስጥ ያሉና በዕድሜ የገፉ ባሎች ያሏቸው ሴቶችም በአብዛኛው ሹገር ማሚነቱን ይከውኑታል፡፡ እነዚህ ሴቶች የትላልቅ ቡና ቤቶች፣ ሆቴሎች፣ ሱፐር ማርኬቶችና ድርጅቶች ባለቤቶች ናቸው፡፡ በድርጅቶቻቸው ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ጥሩ ቁመና ያላቸው፣ ተግባቢ ወጣቶች ሹገር ማሚዎቹ አይን ከገቡ አበቃላቸው፡፡ በገንዘባቸው ሃይል አንበርክከው የወሲብ እስረኞቻቸው ማድረጉን ያውቁበታል፡፡ በራሳቸው ቤት፣ ወይም ቤት ገዝተው አሊያም ተከራይተው ፍላጐታቸውን ሁሉ እያሟሉ የሚያስቀምጧቸው ጐረምሶች፤ ሹገር ማሚዎቹን እንደ ኮረዳ እያሽኮረመሙ የወጣትነት ትኩስ ፍላጐትና ስሜት እንዲሰማቸው ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
በአብዛኛው በሹገር ማሚዎች የተያዙ ወንዶች፤ ከ“ሚስቶቻቸው” ጋር አብረው በአደባባይ እንደ ልብ መታየትን አይፈልጉም፡፡ ይህ ደግሞ ሹገር ማሚዎቹ እንደ ፍላጐታቸው በየአደባባዩና በየመዝናኛ ቦታው ከ “ጐረምሳቸው” ጋር በፍቅር ለማበድ እንዳይችሉ ያደርጋቸዋል፡፡ አብይ ታሪኩ (ስሙ የተቀየረ) ስለ ሹገር ማሚው ሲናገር፤ በተለየዩ መዝናኛ ቦታዎች ላይ ከእኔ ጋር አብሮ መታየት እንዲሁም በየአደባባዩ በማቀፍና በመሣም ፍቅሬን እንድገልፅላት ትፈልጋለች፡፡ ይህ ደግሞ እኔ ፈፅሞ የማልወደውና የማልፈልገው ጉዳይ ነው” ሲል ገልፆታል፡፡ አብዛኛዎቹ ሹገር ማሚዎች፤ ለፍቅረኞቻቸው ፈፅሞ ነፃነትን አይሰጡም፡፡ ከእኔ ከተለየ ሌላ ሴት (ወጣት) “ይጠብሳል” ብለው ስለሚያስቡ የ “ጐረምሶቻቸውን” ውሎ መከታተል ይፈልጋሉ፡፡ አስር ጊዜ እየደወሉ “የት ነህ?” የሚል ጥያቄ ማቅረባቸውም የተለመደ ነው፡፡ ከወንድ ጓደኞቻቸዉ ጋር እንኳን ቢሆን ለረዥም ጊዜ እየተዝናኑ እንዲቆዩ አይፈቀድላቸውም፡፡ ከሹገር ማሚዎቻቸው ጋር በጊዜ ሂደት ተስማምተው በፍቅር የወደቁ፣ ተጋብተው ህጋዊ ትዳር የመሰረቱም በርካታ ወጣት ወንዶች አሉ፡፡
“ስንጀምር በዚህ መልኩ ግንኙነታችን ይቀጥላል ወይም ዘላቂነት ይኖረዋል ብዬ አልነበረም፡፡ በሂደት ግን በቃ ተመቸችኝ ፤ስንጀምር የነበሩን በርካታ ልዩነቶች እየጠፉ ፍላጐታችን እየተቀራረበ ሄደ፡፡ ታምኚኛለሽ--- ድብን ያለ ፍቅር ያዘኝ፡፡ የእንጋባ ጥያቄውን ያቀረብኩላት እኔ ነኝ፡፡ ከዚህ በኋላ ልጅ የማግኘት ተስፋ እንደሌለኝ ባውቅም ብዙ ስሜት አልሰጠኝም፡፡ የምትወደድ አይነት ሴት ነች፤ ተመችታኛለች፡፡ አሁን እንኳን ከተጋባን ሶስት ዓመት አልፎናል፡፡ የእውነት ነው የምወዳት” ዘውዱ (ስሙ የተቀየረ) ስለ ሹገር ማሚው የተናገረው ነው፡፡
ሹገር ማሚዎች በአብዛኛው የሚጠሉት ነገር ከሹገር ቤቢዎቻቸው ጋር በመዝናኛ ቦታዎች ሲሄዱ “ልጅሽ ነው?” የሚሉ የጓደኞቻቸውን ጥያቄ ነው፡፡ እንዲህ እየተባሉም ቢሆን ሹገር ቤቢዎቻቸው ተለይተዋቸው እንዲቀሩ አይፈልጉም፡፡ ዛሬ ዛሬ በርካታ ወጣቶች፤ ሹገር ማሚዎችን እያሳደዱ መተዋወቅና ማጥመዳቸው የተለመደ ተግባር እየሆነ ነው፡፡ ከሹገር ማሚዎቻቸው የሚያገኙትን ገንዘብ የዕድሜ እኩያዎቻቸውን (ፍቅረኞቻቸውን) ለማዝናናት ይጠቀሙበታል፡፡ በሹገር ማሚዎቹ ለመመረጥና መስፈርቶቻቸውን ለማሟላት ወጣቶቹ ትግል ይዘዋል፡፡ ሹገር ማሚዎቹ በአብዛኛው ሰውነታቸው ደልደል ያለ ተጫዋችና ተግባቢ ወጣት ወንዶችን ለፍቅረኝነት ይፈልጋሉ፡፡ ሹገር ማሚዎቹ እነሱ የሚፈልጉትን አይነት አገልግሎት እየሰጡ አብረዋቸው የሚዘልቁ ወጣቶች የት እንደሚገኙ ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ ለዚህ ተግባር ተመራጩ ቦታ ጅምናዚየሞች፣ ማሳጅ ቤቶች፣ ሲኒማ ቤቶችና ናይት ክለቦች ናቸው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ሹገር ማሚዎች በአገናኝ ደላሎች አማካኝነት የፈለጉትን ወጣት ከእጃቸው ለማስገባት አይቸገሩም፡፡ እድሜ ለቴክኖሎጂ! ዛሬ ደግሞ ሹገር ማሚዎች የፈለጉትን አይነት ወጣት የሚያገኙበትና የሚቀጣጠሩበት ድረገፅ ተከፍቶ ሥራውን በስፋት እየሰራ ይገኛል፡፡ Friendfinder:sugermummy tips.com, Adult friend finder seeking arrengment.com የተባሉት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ዛሬ ዛሬ ከታዋቂ አርቲስቶቻችን መካከል በሹገር ማሚ ወጥመድ ተይዘው ተፈላጊውን አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ወጣቶች እንዳሉም ይነገራል፡፡ ከዕድሜ ጋር ግብግብ የተያያዙት ሹገር ማሚዎች፤ የዕድሜያቸው ጀንበር አዘቅዝቃ ይህቺን አለም ከመሰናበታቸው በፊት ያሻቸውን ለማድረግ፤ የፈለጉትን ለመፈፀም ትግል ይዘዋል፡፡ ወጣት ወንዶቹም (ሹገር ቤቢዎቹ) የኢኮኖሚ ችግራቸውን የሚቀርፉላቸውን ሹገር ማሚዎች ለመንከባከብና ለማስደሰት እየተጉ ይገኛሉ፡፡

Published in ባህል

Progress in a country is measured not by industry or infrastructure or the wealth that its citizens possess, but by the quality of life they lead. Civilization on the other hand, is measured by the quality of character of the citizens. The strength of a society is its social capital.
የአንድ ሐገር እድገት የሚለካው ባሏት ኢንዱስትሪዎች እና በዘረጋቻቸው መሰረተ ልማቶች ወይም ዜጎቿ ባፈሩት ሃብት ሳይሆን በሚመሩት የተሻለ ሕይወት ነው፡፡ የስልጣኔም መለኪያው የዜጎች የምግባር ጥራት ነው፡፡ የአንድ ማሕበረሰብ ጥንካሬም በእጁ ያለው ሶሻል ካፒታል ወይም መልካም እሴት ነው፡፡
ከላይ የቀረበው የእንግሊዝኛ ሃሳብና ተቀራራቢ ትርጉሙ ታዋቂው ሕንዳዊ ጸሃፊ ሼቭ ኬራ፤ “ፍሪደም ኢዝ ኖት ፍሪ” በተሰኘው መጽሐፉ ላይ ያሰፈረው ነው፡፡ ይሄንን ሃሳብ እያሰላሰልኩ በእርግጥ ዛሬ ኢትዮጵያውያን ያለን ትልቁ የጋራ እሴት ምንድን ነው? የሐገር ፍቅር፣ መረዳዳት፣ መከባበር ወይስ ምን? ስል ራሴን ጠየቅሁ፡፡ መልስ ብፈልግም ያላገኘሁለት ጥያቄ ሆነብኝ፡፡ የሀገር ፍቅር፣ መረዳዳት፣ መከባበር… የነበሩን ግን እያጣናቸው የመጡ እሴቶቻችን እንደሆኑ ይሰማኛል፡፡ ከእነዚህ ሃሳቦች በተቃራኒ ገንዘብ ከሁሉ በላይ ነግሶ የትኛውም መንገድ ገንዘብ ጋ እስካደረሰ ድረስ ብዙ ዜጎች በመንገዱ ለመጓዝ የሚደፍሩባት፤ እውነተኛ ስሜት የወለዳቸው መረዳዳትና መከባበር እየሸሿት ያለች እና “የሰረቀ የድርሻውን አነሳ” እየተባለ የሚሞገስባት ሃገርም ሆናብኛለች፡፡ የኋላ ታሪካችን እንዲህ ነበርን? ሳናውቀው በእጃችን ያለውን እሴትስ እያጣን አይደለምን?
ለዚህ ሁሉ መነሻዬ ሕገወጥ ስደትን በተመለከተ በቅርቡ ሲነሱ የነበሩ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ሃሳቦቹ በመነሳታቸው ተቃውሞ የለኝም፡፡ የአንድም ሰው ሕይወት በሕገወጥ ስደት እንዳያልፍ ትልቁ ምኞቴ ነው፡፡ ምኞቴ ምኞት ብቻ ሆኖ እንዳይቀር የሚያሰጋኝ ግን ለሕገወጥ ስደቱ ጆሯችን እስኪደነቁር ድረስ የምንሰማው፤ “ሕገ ወጥ ደላሎች ቀዳሚ ምክንያት ናቸው” የሚለው ግራ ቀኙን ያልተመለከተ የድፍረት አባባል ነው፡፡ ድፍረቱ የሚመነጨው ሕገ ወጥ ደላሎችን ምክንያት አድርጎ ከማቅረቡ አይደለም፡፡ በዘወርዋራው ሕገ ወጥ ደላሎች ላለፉት በርካታ አመታት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን አግዘው፣ በሺህ የሚቆጠሩትን ለሞት ሲያቀብሉ ዝም ብዬ ተመልክቻለሁ፤ በሃገር ውስጥ ያሉ ሕገወጥ ደላሎችን መቆጣጠር ተስኖኝ ነበር ብሎ በአደባባይ ከማወጁ ላይ ነው፡፡ ሕገ ወጥ ደላሎች ለስደቱ አስተዋጽኦ የላቸውም ብዬ አልደመደምኩም፡፡ በግሌ ያነጋገርኳቸው ብዙ ተጓዦች ለደረሰባቸው መከራ ሁሉ የደላሎቹ እጅ እንዳለበት ነግረውኛል፡፡

ሊዋጥልኝ ያልቻለው ግን የሚገባውን ያሕል መስራት ተስኖት ለአመታት በቸልታ ሲመለከት የነበረው መንግስት፤ ለዚህ ሁሉ ምስቅልቅል ሕገ ወጥ ደላሎችን በዋነኛ ምክንያትነት ለማቅረብ ሲጣደፍ ማየቴ ነው፡፡ ከልብ አስቦ የችግሩን መንስኤ ካላወቁ ከመፍትሄው መድረስ አይቻልምና የተሰማኝን ልተንፍስ ብዬ ነው፡፡
ሕገወጥ ስደት፤ በሃገራችን በእጅጉ ተባብሶ የታየው በስልጣን ላይ ባለው የኢህአዴግ ዘመነ መንግስት ነው፡፡ የደረጃው ልኬት በሀገራችን ያለው “ሰላም” ነው፡፡ ሰላምን በትምእርተ ጥቅስ ውስጥ መክተቴ የሰላምን ትርጉም ጦርነት ካለመኖሩ ጋር አቻ ተደርጐ እንዳይተረጐም ነው (peace is not the absence of conflict) ጦርነት በሌለባት ሀገር፣ ድሕነት ሰላም የነሳው በርካታ ኢትዮጵያዊ ይኖራልና፡፡ ከሶስት አመት በፊት የወጣ የስደተኞች ሪፖርት፤ ከኢትዮጵያ የሚሰደዱ ሰዎች ቁጥር፣ ከመንግስት አልባዋና በጦርነት ከምትታመሰው ሶማሊያ ከሚሰደዱ ሰዎች ቁጥር ልቆ ማንበቤን አስታውሳለሁ፡፡

እንዴት እንዲህ ሊሆን ቻለ ብሎ መጠየቅ ተገቢ የሚሆነው በዚህ ጊዜ ነው፡፡ ደርግ ስልጣን ላይ በነበረበት ዘመን፣ በፖለቲካ የተቧደኑ እና እርሱን ለመቃወም የተነሱትን በማሳደድ በርካቶች የሱዳንን በርሃ አቋርጠው እንዲሰደዱ ምክንያት ሆኗል፡፡ የእርስ በእርስ ግጭቱ ያሰደዳቸው ሰዎች ቁጥር ግን በኢህአዴግ የስልጣን ዘመን ከተሰደዱና ከሚሰደዱ ሰዎች ጋር ፈጽሞ የሚነጻጸር አይደለም፡፡ ታዲያ ከሃያ አመታት በፊት በጦር መሳሪያ የታጀበ ግጭት ካሳደደው ኢትዮጵያዊ፣ በጦርነት አልባው በዚህ ጊዜ የተሰደደው ቁጥር እንዴት ሊበዛ ቻለ? ለመብዛቱስ ሕገ ወጥ ደላላ እንዴት ቀዳሚ ምክንያት ይሆናል? ይሁን ቢባል እንኳን ደላላ በቀላሉ ልቡን የሚያሸፍተው ሕዝብስ እንዴት እንዲህ ሊበዛ ቻለ? ከደላላው በላይ በራሱ ማወቅ የተሳነው፣ የሰማውን ብቻ የሚያምን ብዙ ሰው አለን ማለት ነውን? ህገወጥ ደላሎችን በዋና ምክንያትነት የሚያቀርቡ ወገኖች ሊመልሱልን የሚገባቸው ጥያቄዎች ናቸው፡፡
ሶሻል ካፒታል እና ሕገወጥ ደላላ
በመግቢያዬ ያነሳሁት ሺቭ ኬራ፤ የአንድ ሃገር እድገት የሚለካው በዘረጋቻቸው መሰረተ ልማቶች ወይም በዜጐችዋ የሀብት መጠን ሳይሆን በእጅ ባለው፣ ዜጐችዋ በሚጋሩት መልካም እሴት ነው የሚለው አባባል ለአሁን አጀንዳዬ ትልቅ ሃሳብ ሆኖልኛል፡፡ ከጋራ እሴቶች አንዱ ደግሞ የሀገር ፍቅር ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ በእርግጥ ይሄ ሁሉ ስደተኛ ለማመን የሚከብድ አደጋ ከፊቱ እየጠበቀው በረሐ እና ባሕር የሚያቋርጠው፣ በሃገር ከመኖር ሞትን የሚመርጠው፣ ከየትኛውም ምክንያት በላይ በሕገወጥ ደላላ እየተታለለ ነው ብሎ መቀበል ይከብዳል፡፡ ለሀገሩ ያለው ፍቅር እና ተስፋ ተሟጥጦ እንዳልሆነ ማን ጠየቀው፡፡ በኢትዮጵያና በመካከለኛው ምስራቅ ግንኙነት ላይ ጥናት የሚያደርጉት አደም ካሚል የተባሉ ተመራማሪ ለ “ሰንደቅ” ጋዜጣ መጋቢት 11 ቀን 2005 ዓ.ም እትም በሰጡት ቃለ ምልልስ፤ በሕገ ወጥ መንገድ የሚጓዙ ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያን አይወዷትም ብለዋል፡፡ ፀሐፊው ሃሳባቸውን በማስረጃ ሲያረጋግጡ፤ በ2012 እ.ኤ.አ ብቻ 338‚000 ኢትዮጵያውያን በህገወጥ መንገድ ሳኡዲ ገብተዋል፡፡ ይህ ቁጥር የተያዙትን ብቻ የሚገልፅ ነው፡፡ የፀሃፊውን ሃሳብ ይበልጥ ያጠናከረው ባለፈው ዓመት በህጋዊ መንገድ ለሐጂና ኡምራ ሳኡዲ ገብተው ያልተመለሱት ሰዎች ቁጥር ነው፡፡ 36ሺ ተጉዘው የተመለሱት 9997 ብቻ ነበሩ፡፡ ታዲያ ይሄንን ቁጥር እያነበቡ ከሕገወጥ ደላላ ሌላ ያሉ ምክንያቶችን በደንብ መፈለግ አይገባምን?
አንገት የሚያስደፋው ይሕ ሕገ ወጥ ስደት ገደቡን ከሳተና በርካታ ኢትዮጵያውያን ሕይወትና አካላቸውን ካጡ በኋላ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመንግስት የመገናኛ ብዙሐን የምንሰማውና የምናያቸው በጉዳዩ ላይ ያተኮሩ ፕሮግራሞች አስፈላጊ ቢሆኑም ከልብ የሆነ ጥረትን እና ሕገወጥ ስደትን ለማቆም ቁርጠኝነትን የሚያሳዩ፣ ከሚፈለገው ውጤትም የሚደርሱ አይመስሉኝም፡፡ ፖለቲካዊ ምክንያትና ተጠያቂነት ያለበት ትልቅ ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ሃላፊነት የተሰጠው መ/ቤት እስከዛሬ የተጓዘበትን፣ በጉዞውም ለውጥ ከማምጣት ይልቅ የስደቱ መጠን እንዲጨምር የጨመረበትን ምክንያትና የአሰራር መንገዱን ጭምር መፈተሽ ይኖርበታል፡፡ መስሪያ ቤቱን የሚመሩት ሰዎች አልቻሉምና የሚችል ሰው ሊፈለግ ይገባል፡፡ የመደመጥ አቅሙ ያላቸው ባለስልጣናትም የሃይማኖት አባቶች ጭምር ለቁጥር የሚያስደነግጥ የጅምላ ሞት ለሰማንባቸው “ሃገሬ እነዚህን ሁሉ ልጆችሽን በማጣትሽ አዝነናል” ሲሉ የሐዘን ቀን ሲያውጁ መስማትን እንፈልጋለን፡፡ ከልባቸው ለልባችን መቅረባቸውን የምናውቀው ያኔ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ የፈረንጅ ሃገር ናፋቂ የሆንበትን፣ አማርኛ ቋንቋ መናገር በአንዳንድ ት/ቤቶች በአደባባይ ሲከለከል የሰማንበትንና የመንግስትን ዝምታ ያየንበትን ይሄንን ጊዜ ቆም ብሎ ማስተዋል ይጠይቃል፡፡ አንዳንድ ባለስልጣኖቻችንና የከተማችን ሃብታሞች ነፍሰጡር የሆኑ ሚስቶቻቸውም፣ ልጆቻቸውም የአሜሪካና አውሮፓ ዜግነት አግኝተው እንዲወልዱ፣ ወደዚያው የመሰደዳቸውን ምክንያት እንዲሁም ኢትዮጵያዊነት ገሸሽ የተደረገበትን እንቆቅልሽ መፍታት ያስፈልጋል፡፡ የገዢው ፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን ለስራ፣ ለትምሕርት እድል እና ለስልጣን (የሕዝብ አገልጋይነት) መስፈርት ሆኖባቸው ያኮረፉ ዜጎችንም ቁጥር እና ስሜት ማጥናት ያስፈልጋል፡፡ የዚህ ሁሉ መደምደሚያው ጥያቄ ውስጥ የወደቀ የሚመስለውን የሃገር ፍቅር ስሜት መልሶ ለማግኘት ይጠቅማል፡፡ ያኔም ያዋረደንን የሕገወጥ ስደት ትክክለኛ ምክንያት መለየት እንችል ይሆናል፡፡ በቀናን!

ፍ/ቤቱ በሁለት መዝገቦች ላይ ለመጨረሻ ጊዜ የምርመራ ቀጠሮ ሰጠ
በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኘው የከፍተኛ ባለሀብቶች ኩባንያዎችን የማስተዳደር ጉዳይ የፀረሙስና ኮሚሽን መርማሪዎችንና ተጠርጣሪ ባለሃብቶችን እያከራከረ ሲሆን ፍ/ቤቱም በጉዳዩ ላይ ትዕዛዝ ለመስጠት ለማክሰኞ ሐምሌ 30 ቀን 2005 ዓ.ም ቀጥሯል፡፡

ኮሚሽኑ የአምስቱን ኩባንያዎች ንብረት፣ ኮሜርሻል ኖሚኒስ እንዲያስተዳድርለት ለፍ/ቤቱ ማመልከቱ የሚታወስ ሲሆን ሃሙስ በዋለው ችሎት ፍርድ ቤቱ በተመረጠው ድርጅት ኩባንያዎችን የማስተዳደር አቅም ላይ ጥያቄ አንስቷል፡፡ የኮሜርሻል ኖሚኒስ ልምድ በአብዛኛው ከገንዘብ መሰብሰብ እና ክፍያ መፈፀም እንዲሁም ከአክሲዮን ማሻሻጥና ከመሳሰሉት ጋር የሚገናኝ ሆኖ ሳለ፣ እነዚህን በተለያዩ የምርትና የአገልግሎት ስራ ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች እንዲያስተዳድር እንዴት ተመረጠ የሚል ጥያቄ ለኮሚሽኑ አቃቤ ህግ አቅርቧል፡፡ የኮሚሽኑ አቃቤ ህግም ኮሜርሻል ኖሚኒስ በተመሳሳይ የሚያስተዳድራቸው ሌሎች ኩባንያዎች መኖራቸውን በመግለፅ፤ የድርጅቱን የማስተዳደር ብቃት አጥንተንና አምነንበት ነው የመረጥነው ብሏል፡፡

አቃቢ ህግ አክሎም “የተሰጠን ቀን አጭር ስለነበር ኮሜርሻል ኖሚኒስን ሳናነጋግር ብቃቱን ካለፉት ልምዶቹ በማረጋገጥ ነው ያቀረብነው” ብሏል፡፡ ፍ/ቤቱም በድጋሚ የማስተዳደር ብቃቱ በሚገባ ተመርምሯል ወይ የሚል ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን የኮሚሽኑ አቃቤ ህግ በተሰጠን አጭር ጊዜ ስለ ድርጅቱ ብቃት ማስረጃ አሰባስበን አቅርበናል በማለት ምላሽ ሰጥቷል፡፡
ከኩባንያዎቹ መካከል በእነ አቶ መላኩ ፋንታ መዝገብ ተካትተው ጉዳያቸውን እየተከታተሉ የሚገኙት አቶ ከተማ ከበደ በባለቤትነት የሚያስተዳድሩት ኬኬ ሃላፊነቱ የተወሠነ የግል ማህበር፣ ግለሰቦችን ለአስተዳዳሪነት መርጦ ያቀረበ ሲሆን በተመሳሳይ ፍ/ቤቱም በነዚህ ግለሠቦች የብቃት ጉዳይ ላይ ጥያቄ አንስቷል፡፡ በእለቱ በችሎቱ የተገኙት የድርጅቱ ተወካይም ድርጅቱ ቡና ወደ ውጪ ከመላክ፣ ማሽነሪ ከማስመጣትና ከጨርቃጨርቅ ምርት ጋር የተያያዙ በርካታ ስራዎች ያሉት መሆኑንና የሰው ሃይሉ በርካታ በመሆኑ ይህን ሃላፊነት ወስደው ማስተዳደር ይችላሉ ብለን መርጠን አቅርበናል ብለዋል፡፡
ሌላው በእነ አቶ ገ/ዋህድ መዝገብ ስር ተካትተው ጉዳያቸውን እየተከታተሉ የሚገኙት አቶ ነጋ ገ/እግዚአብሔር በባለቤትነት የሚያስተዳድሩት ነፃ ትሬዲንግ በራሱ በኩል ተመርጦ የቀረበ አስተዳዳሪ አለመኖሩን ፍ/ቤቱ አስታውቆ፤ ለጠበቆቹ “በምን አይነት ሁኔታ እንዲቀጥል ትፈልጋላችሁ?” የሚል ጥያቄ አቅርቧል፡፡ ጠበቆቹ ቀደም ሲል በነበረው ችሎት ከኮሚሽኑ ጋር በጋራ አጥንተን እንድንመጣ በታዘዝነው መሠረት ጉዳዩን በጋራ የተወያየንበት ቢሆንም ከተስማማንበት ውጪ ኮሚሽኑ ኮሜርሻል ኖሚኒስን መርጦ አቅርቧል ብለዋል፡፡
ቀደም ሲል ከኮሚሽኑ ጋር የተነጋገሩበትም ችሎቱ ላይ ተለዋጭ ቀጠሮ እንጠይቃለን፤ ከዚያ በኋላ ተስማምተን እንሾማለን የሚል እንደነበር ለፍ/ቤቱ ያመለከቱት ጠበቆቹ፤ በኩባንያው በኩል በአጭር ቀን ውስጥ ብቃት እና ዋስትና ያለውን አስተዳዳሪ አካል አጣርቶ መርጦ ማቅረብ ከባድ ነው ብለዋል። በአሁን ሠአት ኩባንያው ወጥ የሆነ አስተዳደር እንዳለው የተናገሩት ጠበቆቹ፤ በቀጣይ ከየመስሪያ ቤቶቹ የተውጣጣ ኮሚቴ ተቋቁሞ እንዲያስተዳድር ሃሣብ አቅርበዋል፡፡
ፍ/ቤቱ እነዚህን አቤቱታዎች እና ምላሾች ካዳመጠ በኋላ “ለምንድን ነው ተነጋግራችሁ በጋራ መወሠን ያልቻላችሁት?” ሲል የኮሚሽኑ አቃቤ ህግ ጠይቋል፡፡ አቃቤ ህግም ኬኬ ሦስት ግለሠቦችን መርጦ ያቀረበ ቢሆንም ያቀረቡት ግለሠቦች እዚያው በኩባንያው ሠራተኛ የነበሩ በመሆናቸው ገለልተኛ ሆነው ማስተዳደር እንደማይችሉ ስለሚታመን መስማማት አልቻልንም ብሏል፡፡ ነፃ ትሬዲንግን በተመለከተም በሃሣብ ደረጃ እንጂ በፅሁፍ ምርጫቸውን አላቀረቡልንም በማለት ገልጿል። ፍ/ቤቱም እነዚህን የግራ ቀኝ ክርክሮች ካዳመጠ በኋላ፣ ኮሚሽኑና የተጠርጣሪ ባለሃብቱ ኩባንያዎች ጠበቆች የመነጋገርና የማጥናት ስራውን በጋራ እንዲቀጥሉ በማሣሠብ እንዲሁም ፍ/ቤቱ ራሱ ጉዳዩን የማስጠናት አማራጭ እንዳለው በማስገንዘብ በጉዳዩ ላይ ትዕዛዝ ለመስጠት ለማክሠኞ ሐምሌ 30 ቀን 2005 ዓ.ም በድጋሚ ተለዋጭ ቀጠሮ ሠጥቷል፡፡
በሌላ በኩል በእለቱ ፍ/ቤቱ በእነ ተመስገን ስዩም እና በእነ መልካሙ እንድሪያስ መዝገብ ስር የተካተቱ ተጠርጣሪዎችን ጉዳይ የተመለከተ ሲሆን ለመርማሪ ቡድኑ በሁለቱም መዝገቦች ለመጨረሻ ጊዜ የስምንት ቀን የምርመራ ቀጠሮ ፈቅዷል፡፡
መርማሪ ቡድኑ በእነዚህ ሁለት መዝገቦች ላይ የተለያዩ የምርመራ ስራዎችን በተሠጠው 10 ቀን ውስጥ ማከናወኑን አመልክቶ፣ ይቀሩኛል ያላቸውን ተግባራት ከዘረዘረ በኋላ፣ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ የጠየቀ ቢሆንም የተጠርጣሪ ጠበቆች ከዚህ ቀደም የተሠጠው ቀጠሮ በቂ ስለሆነ ሊፈቀድለት አይገባም፣ የክስ መመስረቻ ጊዜ ብቻ ይሠጠው፣ ተጠርጣሪዎች ከ80 ቀን በላይ በእስር ላይ መቆየታቸው የፍርድ ያህል እየታሠሩ እንደሆነ ይቆጠራል የሚሉና ሌሎች ምክንያቶችን በማቅረብ ተከራክረዋል፡፡ ፍ/ቤቱም የመርማሪ ቡድኑ ይቀሩኛል ብሎ በዘረዘራቸው ስራዎች ላይ የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስቷል፡፡
የግራ ቀኝ የቃል ክርክሩን ሲያዳምጥ የቆየው ፍ/ቤቱም፣ በሁለቱም መዝገቦች ለመጨረሻ ጊዜ በማለት የስምንት ቀን ጊዜ ብቻ በመፍቀድ፣ መዝገቡን ለነሐሴ 3 ቀን 2005 ዓ.ም ቀጥሯል፡፡

 

ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት ዘማሪ ወፍ በወጥመድ ተይዛ በቆንጆ ድምጽዋ ትዘምራለች፡፡ ድምፁዋ በጣም ከማማሩ የነሳ ሌሎች ወፎች ሁሉ ፀጥ ብለው ያዳምጡዋታል፡፡
“ስበር እውላለሁ፡፡
ስከንፍ አረፍዳለሁ፡፡
ማን ይየኝ ማን ይስማኝ
መች እጨነቃለሁ?
የምሮጥ ለራሴ፣
የመኖር ለራሴ፣
ይድከመኝ ይመመኝ፣
ራሴ ነኝ ዋሴ፡፡
ሰው ግን ይከፋዋል፣
ጥላዬ ሲያርፍበት
ላይከብደው ላይጐዳው፣
ድንገት ባለፈበት፡፡
ሊያጠምደኝ ይለፋል፤ ጉዳዩ አይገባኝም፡፡
ወፍ ይዞ በማሰር፣ ምን እንደሚጠቀም?
ሽቦ - ቤት ባልገባም፤ መዘመሬ አይቀርም…
ሽቦ ቤት ብገባም መዘመሬ አይቀርም!!”
ይህን መዝሙሯን ሁሌ ማታ ማታ ስታሰማ የሌሊት - ወፍ መጥታ በጥሞና ታዳምጣታለች፡፡ አንድ ቀን እንዲህ ስትል ጠየቀቻት፤
“እመት ወፊት?”
“እመት” አለች ወፊት፡፡
የሌሊት ወፍ - “ሁሌ ስትዘምሪ እሰማሻለሁ”
ወፊት - “አዎን”
የሌሊት ወፍ - “ለተኙት ወፎች?”
ወፊት - “አይደለም”
የሌሊት - ወፍ- “ታዲያ ለማነው?”
ወፊት - “ለራሴ!” አለች ፍርጥም ብላ፡፡
የሌሊት ወፍ - “ግን ሁሌ ማታ ማታ ነው የምትዘምሪው?”
ወፊት - “አዎን”
የሌሊት - ወፍ - “ለምን ቀን ቀን አትዘምሪም”
ወፊት - “ቀን ቀን ችግር ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ቀን ቀን ስዘምር የሰው ልጅ ሰማኝ፡፡ ‘መጥቼ አጠገብሽ ቁጭ ብዬ ላድምጥሽ፡፡ በጣም ቆንጆ ነው የምትዘምሪው’ አለኝ፡፡
እሺ ብዬ አጠገቡ ሆኜ ስዘምር ድንገት ቀጨም አደረገኝ፡፡ ይሄው እዚህ የሽቦ እሥር ቤት ውስጥ ከተተኝ!”
የሌሊት ወፍም፤ “እመት ወፊት፤ ሰው ጠላትሽ መሆኑን ማወቅሽ ድንቅ ነው፡፡ ግን አንድ ነገር ልብ በይ። አንዴ እሥር ቤት ከገባሽ በኋላ ቀንም ዘመርሽ ማታም ዘመርሽ ለውጥ የለውም፡፡ ሰውዬው ለሁለተኛ ጊዜ ሊያጠምድሽ አይመጣም፡፡ ምክንያቱም በእጁ ነሻ!” አለቻት
* * *
የማናቸውም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ቁልፍ ጉዳይ ጊዜ ማወቅ ነው (timing)፡፡ ከዕለቱ አስቀድሞም መንቀሳቀስ፣ ዕለቱ ካለፈም በኋላ መንቀሳቀስ፣ ችግር ላይ ይጥላል፡፡ ትክክለኛ የጊዜ ምጣኔ ያለው የፖለቲካ ሰው፤ ብዙውን የጨዋታውን ሰዓት በእጁ ያስገባ ኳስ ተጨዋች እንደማለት ነው - የሚቀረው ጐል ማግባት ብቻ ነው!
የቅርጫት ኳስ ተጨዋችን ምሳሌ ብናደርገው ደግሞ የመጨረሻዋ ሶስት - ሴኮንድ - ክልል በምትባለው ሳጥን ውስጥ ከገባ፤ ያለው ዕድል ወደ ቅርጫቱ መወርወር ብቻ ነው፡፡ ከዘገየ ቀለጠ፡፡ “ቦታን ደግመን ልንይዘው እንችላለን፡፡ ጊዜን ግን በጭራሽ ደግመን አናየውም” እንዳለው ነው ናፖሊዮን ቦናፓርት፡፡ የጥንቱ የጧቱ ፖለቲከኛ ሌኒንም “Seize the time, seize the gun” ይለዋል፡፡ “ጊዜን ያዝ፣ ጠመንጃህን ጨብጥ!” እንደማለት ነው፡፡
“ለድል የሚያበቃህ፤ አደለም ጀግንነት
አዛዡ ጊዜ ነው፣ በጊዜ እወቅበት!” እንዳለው ነው የአገራችን ገጣሚ፡፡
ባለፈው ሥርዓት ዝነኛ ከነበሩት መፈክሮች አንዱ፤ “ማፍረስ ቀላል ባይሆንም መገንባት የበለጠ ከባድ ነው” የሚል ነበር፡፡ ዕውነት ነው፡፡ የምናፈርሰውን በጊዜ ማፍረስ፣ እምንገነባውን በጊዜ መገንባት፣ ፍፁም ብልህነት ነው፡፡ በእርግጥም ከማፍረስ ይልቅ መገንባት የበለጠ ከባድ ነው፡፡ የምናፈርሳቸው ቤቶች የሚተኩበትን ህንፃ በማሰብ ብቻ ከተጓዝን፣ የሚያመጣውን አፍራሽ ውጤት (Repercussions) ልብ ሳንል እንቀራለን፡፡ ደምረን ማስተዋል አለብን፡፡ “ነገሮች ምድር ላይ ሰላም ሆነው ይታያሉ፤ እሳቱ ያለው ከሥር ነው” ይላሉ ቱርኮች፡፡ ምንጊዜም ተናጠል ሁነቶች አድገው አስተፈሪ የማይሆኑ ይመስሉናል፡፡ ድምር ውጤታቸውን ግን ዐይን ያለው ነው የሚያይ፡፡ ስለዚህ እንይ! እንይ! እንይ! የቅሬታዎች ሥርና ክር፤ የቱን ያህል እንደሚርቅና የቱን ያህል እንደሚከር እናስተውል፡፡ ካፈረስን በኋላ የፈረሰባቸው ምን ሆኑ? በፈረሰው ቦታ ላይ ምን ተካን? ብለን ደጋግመን እንጠይቅ!
“ብዙዎች የነዳጅ ታንካቸውን ለመሙላት ሲጨነቁ ሌሎች በዓለም ዙሪያ ያሉ ደግሞ ሆዳቸውን ለመሙላት ይታገላሉ፡፡ ይሄ ደግሞ ከቀን ቀን እየባሰ፣ ከቀን ቀን እየከፋ ነው የመጣው” ይላሉ፤ የዓለም ባንኩ ፕሬዚዳንት ሮበርት ዞሊክ፡፡ (ዳምቢሣ ሞዮ)
የኑሮ ልዩነት ክፍተት እየሰፋ፣ ጥቂቶች እየተመቻቸው ብዙዎች እየተራቡ የሚሄዱበት ሁኔታ ውሎ አድሮ ጦሱ አይጣል ነው፡፡
ዛሬ ሰላም የሚመስለን ጐዳና ነገ በብሶተኛ ይሞላል፡፡ ጐርፉ መቼ እንደሚሞላ አናውቅም፡፡ የጐርፉን ምንጭ ግን እናውቃለን፡፡ እሱን ለማድረቅም እንችላለን - ልብ ካለን! ነገሮችን በትክክል አይተን በትክክል ካልፈታናቸው፣ በተለይ ትክክለኛ የጊዜ አጠቃቀም ከሌለን፤ እያደር ከድጡ ወደማጡ እንዳንሄድ፣ ወይም እንደዱሮው አነጋገር “ወጣ ወጣና እንደሽምበቆ ተንከባለለ እንደሙቀጫ” ዓይነት ሁኔታ እንዳይገጥመን፤ በእጅጉ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ መተው ያለብንን መተው፣ በጊዜ መራመድ ያለብንን መራመድ ያሻናል፡፡ አለበለዚያ የትግሪኛው ተረት እንደሚነግረን፤ “ዘወር ካለማለት ነገሩ ሰፋ፣ ቶሎ ካለመሻገር ጐርፉ ሞላ”፤ ማለት ይሆናል ትርፋችን፡፡

Published in ርዕሰ አንቀፅ

እስከ ሐምሌ 30 ክስ ይመሠረትባቸዋል
ከመሬት ጉዳይ ጋር በተያያዘ በፌደራል ስነምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሲፈለጉ የነበሩት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ቃሲም ፊጤ በቁጥጥር ስር ውለው በትናንትናው እለት በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ኛ ወንጀል ችሎት ቀረቡ፡፡ የኮሚሽኑ አቃቤ ህግ ክሱን እስከ ሐምሌ 30 እንዲያቀርብ ታዟል፡፡ 

የፌደራሉ የስነምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ከአቶ ቃሲም ፊጤ በተጨማሪ ቀደም ብሎ በቁጥጥር ስር ባዋላቸው የአስተዳደሩ የመሬት ልማት ቡድን መሪ አቶ በቀለ ገብሬ እና የዚሁ ክፍል ኦፊሰር አቶ ገብረየሱስ ኪዳኔ ላይ ምርመራ እያከናወነ የቆየ ሲሆን ከትላንት በስቲያ አቶ ቃሲም ፊጤን በቁጥጥር ስር አውሎ ትናንት ፍ/ቤት ካቀረበ በኋላ፣ የሶስቱም ተጠርጣሪዎች ጉዳይ በአንድ መዝገብ መታየት ስላለበት ክስ የመመስረቻ ቀጠሮ እንዲሰጠው ብቻ ጠይቋል፡፡
አቶ ቃሲም ፊጤ የተጠረጠሩበትን ወንጀል ፍ/ቤቱ በንባብ ያሰማ ሲሆን የክሱ ፍሬ ሃሳብ፤ በቦሌ ክፍለ ከተማ በቀድሞ ወረዳ 17ቀበሌ 03 ውስጥ የሚገኝን ንብረትነቱ የኢንጅነር ግርማ አፈወርቅ የሆነን 500 ካሬ ሜትር ቦታ በመመሳጠር ለሌላ ግለሰብ እንዲሰጥ በማድረግና በዚህም ከ4 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት በግል ተበዳይ ላይ አድርሰዋል የሚል ነው፡፡
የኮሚሽኑ መርማሪ የተጠርጣሪዎቹን ቃል መቀበሉንና መረጃዎችንም ማሰባሰቡን በመግለጽ የክስ መመስረቻ ቀጠሮ ጠይቋል፡፡
ተጠርጣሪው አቶ ቃሲም በበኩላቸው፤ ጉዳዩ በማጣራት ሂደት ላይ ሆኖ አመት እንዳለፈው በማስታወስ እሳቸው ውጭ ሃገር ስልጠና ላይ ቆይተው ከተመለሱ በኋላ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስረድተዋል፡፡ “ወደ ውጭ የሄድኩት ጉዳዩን እያወቅሁ ነው” ያሉት ተጠርጣሪው፤ የዋስትና መብታቸው ተከብሮ ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ጠይቀዋል።
በዋስትና ጥያቄው ላይ መርማሪው ያላቸውን አስተያየት ሲጠየቁም፤ ክሱ ሲቀርብ የሚጠቀሰው አንቀጽ ከባድ ስለሆነ የዋስትና መብቱን እቃወማለሁ ብለዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ባስተላለፈው ትዕዛዝ፤ የተጠርጣሪውን የዋስትና ጥያቄ ባለመቀበል ኮሚሽኑ እስከ ሐምሌ 30/2005 ክሱን እንዲያቀርብ አዟል፡፡

Published in ዜና

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) በአገሪቱ የተለያዩ ከተሞች በሚገኙ አመራሮችና አባላቱ ላይ በገዢው ፓርቲ የድብደባ፣ የእስርና የግል ሚስጥር መበርበርና በተደራጀ ሁኔታ የመዝረፍ ድርጊት እየተፈፀመ መሆኑን ገለፀ፡፡
ፓርቲው “ህጋዊና ሠላማዊ ትግላችን በህገወጥ የአፈና ስልት ሊደናቀፍ አይችልም” በሚል ትናንት ባወጣው መግለጫ ላይ፤ መንግስት አንድነት ፓርቲን በሀሰት ፕሮፖጋንዳ ከማጣጣልና ያለ አግባብ ከአክራሪነት ጋር ለማቆራኘት ከመስራት አልፎ ሠላማዊ ሠልፎችና ህዝባዊ ስብሰባዎቹ እንዲደናቀፉ አፈና እያደረገበት እንደሚገኝ ገልጿል፡፡
በወላይት ሶዶና በመቀሌ የፓርቲው አመራሮችና አባላት ላይ የመደብደብ፣ የማሰር፣ የግል ሚስጥር የመበርበርና በተደራጀ ሁኔታ የመዝረፍ ድርጊት እንደተፈፀመበት ጠቅሶ፣ ፖሊስ ድርጊቱን አይቶ እንዳላየ ማለፉን ገልጿል፡፡
ፓርቲው በነገው እለት በጂንካ፣ በአርባ ምንጭ፣ በመቀሌ፣ በወላይታ፣ በባህርዳርና በአዲስ አበባ የሚያካሂዳቸውን ሠላማዊ ሰልፎችና ህዝባዊ ስብሰባዎችን ለማደናቀፍ በገዢው ፓርቲ አፈናና ወከባ እየተፈፀመበት እንደሚገኝም ጠቁሟል፡፡
አንድነት ህግን መሰረት አድርጐ እየተንቀሳቀሰ በመሆኑ በነገው ዕለት ሊካሄዱ የታሰቡት ሁሉም ሠላማዊ ሰልፎችና ህዝባዊ ስብሰባዎች በተያዘላቸው እቅድ መሰረት እንደሚከናወኑና ህጋዊ እርምጃው በህገወጥ አፈናው ምክንያት እንደማይቀለበስ በመጥቀስ፣ መላው አገሪቱ ህዝብ በነቂስ ወጥቶ የታፈነ ድምፁን እንዲያሰማ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

Published in ዜና