Saturday, 31 August 2013 12:36

“መንጠልጠል”

ብትል “አፍሮጋዳ” ትዝ አለኝ!
ያለፈው ሳምንቱ የ “እኛና ስብሐት” ፀሐፊ፤ “ጫጫታችሁ ረብሾኛል” ለማለት ብዕሩን ሲያነሳ “መንጠልጠል” የምትለዋን ኃይለ ቃል የተዋሰው ከዚያ ቀደም ባለው ቅዳሜ “ስብሐት ላይ የመንጠልጠል ጣጣ” በሚል ርዕስ ከቀረበ ጽሑፍ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ የሁለቱ ፀሐፊዎች የጽሑፍ ይዘት ኩታ ገጥመነትም “ከእኛ በቀር ሁልሽም በገዘፉ ስሞች ላይ በመንጠልጠል ትራፊ ዝናን የመልቀም አባዜ ተጠናውቶሻል” በሚል ተአብዮ መሞላቱ ነው፡፡ ይህም ከብዕር አጣጣላቸውና ከሃሳብ አሰነዛዘራቸው ያስታውቃል፡፡ ግና ሁለቱም በስብሐት ስም ላይ ከመንጠልጠል ጣጣ የፀዱ ስለመሆናቸው ምንም መተማመኛ የለንም፡፡ ወይም አላቀረቡልንም፡፡
ጋሼ ስብሃትን የተመለከተ ነገር መፃፍና መናገር የሁልጊዜውም ትርጉም “በገዘፈ ስም ላይ የመንጠልጠል አባዜ” ከሆነ እነርሱም ከዚህ የመንጠልጠል ጣጣ የሚያመልጡበት አንዳች “ምስ” በእጃቸው መኖሩን አላሳዩንም። “መንጠልጠል” የብላጣብልጦች ዘዴ ከሆነም ለብልጣብልጥነቱ እነርሱ ብሰው ታይተውኛል፡፡ ሌሎችን “አትንጫጩ” ብለው ከተቆጡ በኋላ፣ እነርሱም ስለ ጋሼ ስብሐት ያሉት ነገር በ “ፀጥታው” መካከል የበለጠ ለመደመጥ ያላቸውን ብርቱ ጉጉት አሳበቀባቸው እንጂ ስለ ስብሐት አስቀድሞ ከተባለው የተለየ ነገር አልነገሩንም፡፡
ይልቁንም ቀድሞ መጪው ፀሐፊ፤ የአገራችንን ኪነጥበብ በተለይም ሙዚቃውንና ሥነ ጽሑፉን የተጣባውን፤ በገዘፉ ስሞች ላይ የመንጠልጠልን አባዜ መፀየፉን፤ “እንግዲህ ይህን ጽሑፍ ልጽፍ የተነሳሁበት መሠረታዊ ምክንያት እኔም ሲያደርጉ እንዳየሁት ስለ ስብሐት የመናገር ዛር ለክፎኝ አይደለም” ቢልም ገና “በቅርበት አላውቀውም” ያለውን ስብሐት፤ ከራሱ ከስብሐት በላይ ሊገልፀው መታተሩን የተመለከተ ሰው፣ እርሱም በዚያው ልክፍት መያዙን አያጣውም፡፡ ዛሬ ግን የምጽፈው ለእርሱ ሳይሆን ለ“አምሣያው” ነው፡፡ ለሌሊሣ ግርማ፡፡
ሃሳብን በመግለጽ ነፃነት የሚያምኑ የሚመስሉ አንዳንድ ሰዎች እነርሱ መስማት የማይሹትን ሃሳብ ለማፈን የሚጐነጉኑትን ሴራ፣ የሚፈነቅሉትን ድንጋይ፤ የሚፈጥሩትን ሰበብ ነፍሴ አጥብቃ ትፀየፈዋለች፡፡ “ሃሳቡ ምንድነው” ከማለት ይልቅ “አሳቢው ማነው” የሚልን ጥያቄ አስቀድመውና ፊታቸው ደቅነው ፍርድ የሚያዛቡ ሰዎችንም ዝም ማለት አልችልም፤ ይልቁንም ለጊዜው ስሙ እንደጠፋኝ እንደዚያ ሰውዬ “ነፃነቴን ስጡኝ፤ አለዚያ ግደሉኝ” በሚል ወኔ ነገሬ ለሚገባቸውም፣ ለማይገባቸውም ሃሳቤን እገልጣለሁ፡፡ በንግግርም፣ በጽሑፍም፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ “ሠፈር” አልመርጥም፡፡ ሰው ያለበት “ሰፈር” ሁሉ ሰፈሬ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ በሰውነቴ እስከተቀበሉኝ ድረስ፣ የመናገርና የመፃፍ ነፃነቱን እስከሰጡኝ ድረስ፡፡
ከሦስት ሣምንት በፊት ጋሼ ስብሐትን አስመልክቶ በተፃፈ ጽሑፍ የተፈጠረብኝን ግርታና፣ የተሰማኝን ስሜት የፃፍኩትም ይህንኑ ነፃነቴን ተገን አድርጌ ነው፡፡ ስፅፍ ደግሞ ሃሳቤን በመግለፄ መርካቴን እንጂ ከመፃፌ ስለማገኘው ሌላ ትርፍ አስቤ አላውቅም፡፡ በእርግጥ አንዳንድ ሰው ሲጽፍ ከዚያ የሚያገኘውን ትርፍና ኪሣራ እያሰላ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ አንዳንድ ርዕሰ ጉዳዮች ግን የበለጠ ትርፍ የሚገኝባቸው መሆኑንም ምሥጢሩን የማያውቁ ከላይ የጠቀስኳቸው ፀሐፊያን ነግረውኛልና አምኛቸዋለሁ፡፡ እኔም ሳላውቀው የዚህ ትርፍ ተጋሪ ሆኜም ይሆናል ጉም ጉምታው የተነሳብኝ፤ ትርፌን ተቀራማች የበዛብኝ፡፡ ከነዚያም አንዱ ሌሊሣ ግርማ ነው፡፡ (ምነዋ ምን በደልኩህ ወንድሜ? ስለምንስ “በስብሐት ላይ ተከራከርኩ” ብዬ ጉራዬን የምነፋበትን ሜዳ ልታሳጣኝ ወደ ግዛቴ መጣህብኝ?)
ሌሊሣ ለ”እኛና ስብሐት” መጣጥፉ አጫፋሪነት “ከአምሳያው” የጽሑፍ ማሣ ላይ የነቀላት “መንጠልጠል” የምትል ቃል እኔን ለመግለጽ የምትመጥን እንደሆነች ተማምኖ ያመጣት ናት፡፡ ቢሆንም እኔን አላስደነገጠችኝም፡፡ “መንጠልጠል የሚለው ቃል የበለጠ የሚገልፀው ጤርጢዮስን ነው” የሚለውን ዓ.ነገር ባነበብኩ ጊዜም “ቤቶች” ድራማ ላይ ያየሁትን ገፀ ባህሪ አባባል አስታውሼ “እኔን ነው?” ብዬ ሣቅሁ እንጂ በፍፁም አልተከፋሁም፡፡
ሆኖም ሌሊሣ “ጤርጢዮስ ሁሌም ለመፃፍ የሆነ ነገር መመርኮዝ ያስፈልገዋል” በማለቱ እስማማለሁ፡፡ ስለዚህም ደግሞ “መንጠልጠልን” ነቅፌ፣ “መመርኮዝን” ደግፌ መልስ እሰጣለሁ (እንደለመደብኝ)፡፡ እውነት ነው ለመፃፍ ብዬ ጽፌ አላውቅም፡፡ ለመፃፍ ከተነሳሁም አንዳች ምክንያት፣ አንዳች መመርኮዣ አግኝቻለሁ ማለት ነው፡፡ ሁሉስ ሰው ቢሆን ለመፃፍ የሚነቃቃበት አንዳች ምክንያት ያስፈልገው የለምን? ሁሉስ ፀሐፊ የክስተት ጥገኛ አይደለም እንዴ? ክስተትን ሳይመረኮዝ ብዕር የሚያነሳ ፀሐፊስ የትኛው ነው? ሩቅ ሳንሄድ አንተ ሌሊሣ ራስህ “እኛና ስብሃት”ን የፃፍከው ከዚያ አስቀድሞ ባነበብከው “በስብሐት ላይ የመንጠልጠል ጣጣ” ላይ ተመርኩዘህ አይደለም እንዴ? ልዩ ክስተትን አድፍጣ የምትጠባበቅ ገጣሚ ነፍስ ያለችው የአዲስ አድማሱ ነቢይ መኮንንስ በዚሁ ሰሞን “ያልነው አልቀረም ጥሩዬ፣ ነገር የገባሽ ሰጐን ነሽ” የሚለውን ልብ የሚያሞቅ “ሦስተኛ” (ቁ.3) ግጥሙን ለጥሩነሽ ዲባባ የገጠመላት የሞስኮን ኦሎምፒክ ድል ተመርኩዞ አይደለም እንዴ? (ምናልባት ጣቢያ ቀላቅዬ ካልሆነ መመርኮዝን የምረዳው እንደዚህ ነው)፡፡
እኔም እንግዲህ አንድ ሰሞን በዚሁ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ሃይማኖታዊ ክርክሮች ተነስተው በነበረ ጊዜ የክርክሩ ንቁ ተሳታፊ ነበርኩ፡፡ ሌሊሣም ይህንኑ ጠቅሷል፡፡ ሆኖም በክርክሩ ሜዳ “ጤርጢዮስ - ከቫቲካን ሁሌም መልስ ነው የሚሰጠው፣ መልሱም ላልተጠየቀበት ጥያቄ መሆኑ የለመድነው አባዜ ነው” ከሚለው ብይኑ የምቀበለው የመጀመሪያውን ዐ.ነገር ብቻ ነው፡፡ “መልስ ሰጪ” ተደርጌ መቆጠሬም እነ ሌሊሣ ጭንቅላት ውስጥ ለሚብላላው ጥልቅ የህይወት ጥያቄ ፍፁም መልስ ያለው በእግዚአብሔር ዘንድ መሆኑን በማመኔ ነው፡፡
በመሆኑም አላፍርበትም፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን የአእምሮዬን ስምምነት አልፎ ወደ ልቤ ዘልቆ የገባውን መለኮታዊ እውነት “መልስ” አድርጌ ማቅረቤንም መቼም ቢሆን የምተወው አይደለም፡፡ መንጠልጠል ካስፈለገኝም የምንጠለጠለው እሱ ላይ ነው፡፡ ሌሊሣ እንዳለው ዞሬ …ዞሬ “የምገነድሰው” አምላኬ ላይ በመሆኑ የ”ነፍሴ ጥሪ”ም እርሱን ለማግነን በመዋሉ እጅግ እኮራለሁ፡፡
በቀረው ግን ለመፃፍ ብዬ “ሳይጠሩኝ አቤት” ያልኩበት አጋጣሚ መኖሩን፣ የገነነ ስም ባላቸው ላይ ተንጠልጥዬ “እዩኝ” ያልኩበትን ርዕሰ ጉዳይ በውል አላስታውስም፡፡ ሃሳቤን ለመግለጽ ምክንያት ከሆነኝ ግን ይሉኝታን ፈርቼ የምተወው ማንም የለም፡፡ ጮክ ብሎ የሚሰማ ያለማመን ጩኸት ካልሰማሁም “መልስ ለመስጠት” አልነሳም፡፡ በዚህ ሰሞንም ሌሊሣን ዕረፍት በሚነሳ መልኩ ለተጀመረው “ጫጫታ” ቆስቋሹ እኔ አልነበርኩም፡፡ በስብሐት ላይ ለመንጠልጠል መገለጫ ልሆን የምችልበትም ምንም ምክንያት የለም፡፡ የእኔ ድርሻ ካለም የ”ዝምታው” ሰምና ወርቅ ተፈልቅቆ እስካየሁት ድረስ በ”ዝምታው” ያስደምመኝ የነበረውን፣ የወዳጄ ሚልኪ ባሻን “ስለ ስብሐት እኔን ጠይቁኝ” ዓይነት ጽሑፍ ለመሄስ መነሳቴ ብቻ ነው፡፡
ያም ከወዳጄ የማልጠብቀውን ስድብ የመጠጣትን ዋጋ አስከፈለኝ እንጂ ስብሐት ላይ “በመንጠልጠሌ” ያተረፍኩት ምንም የለም፡፡ (ሚልኪ ወዳጄ፤ እንዲያ እስከ ዶቃ ማሠሪያዬ ሞልጭኸኝ ስታበቃ “ለጢርጢዮስ መልሴ ዝምታ ነው” ማለትህ ግን እስካሁንም አልገባኝም፡፡)
ሌላውን ወዳጄን ሌሊሣ ግርማን የምለውና የምጠይቀው ደግሞ የሚከተለውን ነው፡፡ “መንጠልጠል” የሚለው ቃል የበለጠ የሚገልፀው እኔን (ጤርጢዮስን) ይሁን፣ ግና በኪነጥበቡ ዓለም በገዘፉ ሰዎች ላይ መንጠልጠል የገንዘብና የዝና ትርፍ የሚያስገኝ ከሆነ፣ አንተስ ለመጽሐፍህ “አፍሮጋዳ” የሚል ርዕሰ ለመስጠት የተነሳህበት ዓላማ ምን ነበር ይሆን? “አፍሮ” ቴዲ አፍሮን፣ “ጋዳ”ም የ “ዴርቶጋዳ” መጽሐፍ ፀሐፊን ይስማዕከን የሚመለከት ነውና፣ ሁለቱ ወጣቶች ደግሞ ለሚያጌጡባቸው ብዙዎች የጊዜው ፈርጦች መሆናቸውን አሳምረህ ታውቃለህና፣ የእነርሱን ስምና ተግባር የሚወክል ርዕስ ለመጽሐፍህ መስጠትህ፣ ብሎም እነርሱኑ መተንኮስህና ማቃለልህ “መንጠልጠልን” የበለጠ የሚገልፀው አይመስልህም? ከእነርሱ ስም በላይ ስምህን ለማግነን ሆን ብለህ ያደረግኸውስ አይደለምን?ይሄ በምን ትዝ አለህ አትለኝም፡፡ ባለፈው ሳምንት “በስብሐት ላይ የመንጠልጠል ጣጣ” ብሎ የፃፈልን ያንተ “አምሣያ”፣ የ”መልክዓ ስብሐት” መጽሐፍን አዘጋጅ አለማየሁ ገላጋይን በስብሐት ላይ በመንጠልጠል ክፉኛ ሲወቅሰው፣ በተቃራኒው ያንተን “አፍሮጋዳ”፣ የዘመናችንን መልክ ማሳያ መስታወት አድርጐ በምሣሌነት ጠቅሶት ተመልክቼ ለካስ ሁላችንም “ተንጠልጣዮች” ነን፡፡

Published in ጥበብ

ካለፈው የቀጠለ
ይህን ካለፈው ፅሑፍ የቀጠለ ምልከታ እንድንጽፍ መነሻ የሆነን መፅሐፉ (“መልክአ ስብሃት”) ውስጥ ያለ አንድ የካርቱን ስዕል ነው፤ ካርቱኑ ስብሃት ላይ የተንጠለጠሉ ሰዎች ያሳያል፡፡ ሰዓሊው ካርቱኑን የሳለው መቼ እንደሆነ ባናውቅም 2004 ብሎ ፈርሞበታል፡፡ ማለታችን ካርቱኑን የሳለው “መልክአ ስብሀት…” ውስጥ ያሉትን ፅሑፎች ረቂቅ በሙሉ አንብቦ ይሁን አይሁን አናውቅም፡፡ እኛ ግን “መልክአ ስብሃት...” ውስጥ ያሉ ፀሐፊዎችን ብቻ ወስደን፣ ከሰላሳዎቹ ውስጥ ምን ያህሉ ስብሃት ላይ ለጉድ እንደተንጠለጠሉበት እናሳያለን፡፡ የምንጠቅሳቸው ፀሐፊዎች መልክአ ስብሃታቸውን የፃፉት ስብሃት እንዴት እንደሚያያቸው (ያያቸው እንደነበር፣ አሁንም የሚያያቸው ይመስላቸው ይሆን እንዴ?) ነው፡፡
ለአንባቢዎች ሌሎች ፀሐፍት ስብሃትን እንዴት እንደሚያዩት ብቻ ሳይሆን፣ሌሎች ፀሐፍትን ስብሃት እንዴት እንደሚያየቸው (ያያቸው እንደነበር) ሊያሳዩን በየበኩላቸው የጣሩትን ማየቱም፣ ሰብሰብ አድርጎ ማቅረቡም አንድ ነገር ነው፡፡ እንዲያ ለማድረግ የሞከሩትን ሰባት ፀሐፍት በንዑሳን ርእሶች እናሳያለን፡፡ ዘናጩ ደራሲ እና ስብሃት (አለማየሁ ገላጋይ) እብዱ ጂኒየስ እና ስብሃት (ከበደ ደበሌ ሮቢ) “አሜሪካዊው” ባለቶክ-ሾው እና ስብሃት (መስፍን ሃብተማሪያም) ወጣት ደራሲ መሆኑ የማይቀረው ሰው እና ስብሃት (ጌታቸው ወርቁ)፣ ሞጋቹ ጠያቂ እና ስብሃት (ተሾመ ገብረስላሴ፣ አባቱ፣እሱ፣ እና ስብሃት (አልአዛር ኬ)፣ የሆነ ሰውዬ እና ስብሃት…በሚሉ፡፡
ይህቺ እኔ እና ስብሃት ብላ ነገር አልተመቸችንም፤ እንዲያውም አንድ ቀልድ አስታወሰችን፤ ስብሃትና አንዱ ናቸው አሉ፤ አንዱ ስብሃትን፡-
“ስብሃት የአምስት መቶ ብር ጥያቄ?” ይለዋል፡፡
“እንስማዋ፡፡”
“የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር ስንት ነው?”
“በርግጠኛ እርግጠኝነት አናውቀውም፤ ግን እንሞክር፡፡”
“ሸጋ፡፡”
“ሁለት ናቸው፡፡” አለ ስብሃት ብዙ ከአሰበ በኋላ፡፡
“ምን?! ሁለት ብቻ?!”
“አንክት!”
“እሺ ይሁን፤ ሁለቱ እነማን ናቸው?”
“እኔ እና ሌሎች፡፡”
ዘናጩ ደራሲና ስብሃት (አለማየሁ ገላጋይ)
የነሐሴ 11 ቀን የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ “ስብሃት ላይ የመንጠልጠል ጣጣ” በሚል ርዕስ የጻፈው መልካም ሰው አባተ ተሳስቷል እንላለን፡፡ መልካም ሰው አባተ እንደጻፈው አለማየሁ ገላጋይ ስብሃትን ቅዱስ አላደረገውም፡፡ ከሁሉም ልቆ ስብሃት ላይ የተንጠለጠለው አለማየሁ እንደሆነ እናውቃለን፤ ግን ቀድሶት ሳይሆን አርክሶት ነው። ምክንያቱም ገጽ 245 ላይ እንዲህ ብሎ ጽፏላ፡- “እንግዲህ ከብዙ መስፈርቶች አንጻር ለተበላሸው የደራሲነት ሰብዕና ምንጭ ሆኖ የምናገኘው ስብሃት ገብረእግዚአብሔርን ይሆናል፡፡”
“በስብሐት የጠፋውን የደራሲነት ስብዕና ፍለጋ” በሚለው ፅሑፉ አለማየሁ ገላጋይ፣ ስለአለማየሁ ገላጋይ እንዲህ ጽፏል፡-
“ደራሲ እንዴት ያለ ቁመና አለው? ብዬ እራሴን የጠየኩበት የመጀመሪያ ገጠመኜ ይሄ ነው፡- 2001 ክረምት ይመስለኛል የሐዋሳው 60 ሻማ የሥነ-ጽሑፍ ክበብ እንግዳ ሆኜ እንድገኝ ጋብዞኛል። ስምምነቴን በቃል ሳረጋግጥ የክበቡ ተወካዮች ለቅድመ-ዝግጅት ስለፈለጉኝ እዚሁ የአዲስ አበባዋ ፒያሳ አንድ ካፌ ውስጥ ተቀጣጠርን፡፡ በአካል ስለማንተዋወቅ በሞባይል ምሪት ለመገናኘት ነበር ተስፋ ያደረግነው፡፡ ጥቂት ዘግይቼ ስለነበረ ይመስለኛል የክበቡ ተወካዮች ደውለው ካፌው በረንዳ ላይ እንደተቀመጡ ነገሩኝ፡፡ እቦታው ስደርስ መንገድ መንገዱን በጉጉት የሚመለከቱ ሁለት ሰዎች አይቼ፣ እነሱ መሆናቸው ገባኝ፡፡ አጠገባቸው ስደርስ በፉክክር መልክ “ያ ነው”፣ “አይ ያኛው ነው” ይባባሉ ነበር፡፡ ጠረጴዛቸውን ከከበቡት ክፍት ወንበሮች አንዱ ላይ ለመቀመጥ ፈቃዳቸውን ጠየቅሁ፡፡ እንድቀመጥ ፈቅደውልኝ ልብም ሳይሉኝ አሁንም መንገዱ ላይ አይናቸውን አነጣጠሩ፡፡
“ያ ነው”
“አይ፣ ያኛው ነው”
እኔን እንዳይገምቱ ያደረጋቸው ሁኔታ ጥያቄ ስለፈጠረብኝ ዝም ብዬ ተቀመጥኩ፡፡ እኔ ስለመሆናቸው የሚጠረጥሯቸው ሰዎች በኑሮ የተጎሳቆሉና ድሎት የማይታይባቸው ነበሩ። የጠረጠሩዋቸው አልፈው ሲሄዱ ደግሞ ሌላ ጠውላጋ ፈልገው “ያውና” ይላሉ፡፡
“ሰው እየጠበቃችሁ ነው?” ስል ጠየኳቸው፡፡
“አዎ፣አዎ” ብለው አሁንም ከቁብ ሳይፅፉብኝ ለጠውላጋ አደን አይናቸውን ጎዳና ላይ ደገኑ፡፡
“እኔ ነኝ” አልኳቸው፡፡
ሁለቱም በመገርም ዞሩ፣በመገረም አተኮሩብኝ፣ በመገረም “አትመስልም፣አትመስልም” አሉኝ፡፡ ጥርጣሬአቸው መታወቂያ እስከመጠየቅ የሚዘልቅ አይነት ነበር፡፡
“እንዴት ዓለማየሁ ገላጋይን ሳልመስል ቀረሁ? ዓለማየሁ ገላጋይ ምን ይመስላል? በፅሑፍ እንዴት ተገምቶ ኖሯል?... ለደራሲ የተሰጠው አንዳች ተመሳሳይ ቁመናና ጠባይ በሁላችንም ውስጥ አለ ማለት ነው?”
ከአለማየሁ ገላጋይ ጽሁፍ የጠቀስነው ረዘመ አይደል? ምን እናድርግ ብላችሁ ነው? ይኸውላችሁ በአለማየሁ ገላጋይ አርታኢነት የተጻፈ “መልክዐ ስብሃት…” እንዲህ ሆነ፡፡ በዚህ ሁሉ ረዥም ጽሁፍ አለማየሁ ያልተጎሳቆልኩ እና ድሎት የሚታይብኝ ነኝ እያለ ነው፡፡ (እንዴት ነው ብዙ ስለማይበላ ሰው መጽሀፍ መጻፍ ያበላል እንዴ?)
አለማየሁ ሌላም ብሏል፡፡
አለማየሁ ገላጋይ በእጅ አዙር ፀጉሩን በየጊዜው እንደሚስተካከል፣ ባለትዳርነት እንደሚስማማው፣ እንደ ነገሩ ሳይሆን ሽክ ለማለት እንደሚለብስ፣ የአምላክ መኖርን እንደማይጠራር፣ የማያጨስ፣ የማይቅም፣ ጫማው ሁሌ የሚወለወል እንደሆነ፣ ጠውላገ ሳይሆን ደጓሳ፣ ንትርክ የሚጠላ እንደሆነ ጽፎልናል፤ በእጅ አዙር፡፡ ጎበዝ ልጅ¡
እብዱ ጂኒየስ እና ስብሃት (ከበደ ደበሌ ሮቢ)
የከበደ ደበሌ ሮቢ ፅሑፍ የወጣለት ስም ወይም ርዕስ “ህያው ስብሃት” ነው ብለናል፡፡ አንድ ጓደኛችን የከበደን ፅሑፍ ካነበበ በኋላ “አይ ከበደ ስብሃትን በጣም አካበደው” አለን፡፡ እኛ ደግሞ እንዲህ አልነው፡- “እራሱን ደግሞ ምን ያህል እንዳከበደ ብታስተውል እንዲህ አትልም ነበር፡፡” አባባላችንን በመረጃ እናስደግፋለን፤ ከበደ የፃፈውን እንጠቅሳለን።
“ተሰድበው የማያውቁ ሰዎች አሉ፤ በፍቅር በተለሰነ የቀልድ መልክ ባለው አቀራረብ እንኳ ተሰድበው የማያውቁ ሰዎች አሉ፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እኔ አንዱ ነኝ፡፡ ጋሼ ስብሃት ባለበት አንዲት በፅሑፍ ጥበብ ዙሪያ ያለች ወዳጅ ምናልባት ለቀልድ ሊሆን ይችላል… ባለጌ… አለችኝ”
“ጋሽ ስብሃት እኔ ባለጌ ነኝ ወይ?” ብዬ ጠየኩት፡፡
“እውነቱን ለመናገር ነው ወይስ ከጉድ ለመውጣት…?” ብሎ ጥያቄዬን በጥያቄ መለሰልኝ፡፡
“እውነቱን ለመናገር….” ብለው፡፡
“…አንተ እብድና ጂኒየስ ነህ እንጂ ባለጌ አይደለህም”
ለአንድ ስብሃትንም ከበደ ደበሌ ሮቢንም ለሚያውቅ ጓደኛችን መፅሐፉ ላይ ስብሃት ለከበደ ደበሌ ሮቢ አለ የተባለውን በጣታችን ጠቆምነው፡- “…አንተ እብድ እና ጂኒየስ ነህ…” አነበባት፡፡
“እናስ?” አለኝ፡፡
“ስለመወድሱ እርሶ ምን እንደሚሉ ለማወቅ ፈልገን ነው፡፡” አልነው፡፡
“የመጀመሪያዋ የመወድስ ቃል ትገባዋለች፣ ትሆነዋለች፤ ይውሰዳት፤ ሁለተኛዋን ግን ቢተዋት መልካም ነው፤ ሸክም ትሆንበታለች እንላለን፡፡” አለን፡፡
ከበደ ደበሌ ሮቢ ትንሽ ዝቅ ብሎ ደሞ እንዲህ ይላል፡-
“ስብሃት ለአብ፡- ራሱ የሚደነቅ ብቻ ሳይሆን ሌሎችን ማድነቅ የሚወድድ፣ በአድናቆት የተመላ፣ ገር፣ ደግና ጨዋ፣ ተዝቆ የማያልቅ ሰው ነው፤”
ይህን የሚለው ቀጥሎ ስብሃት ለሚወረውረለት የአድናቆት ድርጎ ሲያመአቻቸን ነው፤ ለዚህ፡-
“አንተ ገና ልጅ ሆነህ ይሄንን ሁሉ ከየት አመጣኸው ያለኝ ገና እንደተዋወቅን ነው፡፡ … በሌላ ጊዜ “ሩሶን ትመስለኛለህ” አለኝ፤ ሩሶ በነቮልቴር ዘመን የኖረ ፈረንሳዊ ፈላስፋ ነው፤…” (ዣንዣክ ሩሶ አብዶ ነው የሞተው)፤ ከበደ ደበሌ ሮቢ አሁንም ይቀጥላል… “…ውድ ተወዳጅ ወዳጃችን ዘነበ ወላ ቤት ለሰባት ሰዓታት ያህል በመነካትና በከፍታ ስናወራ ከቆየን በኋላ በመጨረሻ፡- “በርናርድ ሾውን ትመስለኛለህ” አለኝ፤ (ይታያችሁ በርናርድ ሾው እንግሊዞች የሚመኩበት ጸሃፌ ተውኔት ነው፤ ከበደ ደበሌ ሮቢስ? ምናልባት የዚያን ቀን ዘነበ ወላ ቤት የሚገርም ትያትር ሰርቶ ይሆናል፡፡)
“አሜሪካዊው” ባለቶክ-ሾው እና ስብሃት (መስፍን ሃብተማሪያም)
የመስፍን ሃብተማርያም ጽሁፍ ርዕስ “ስብሃት ሞቶም ይናፈቃል” ትላለች፡፡ እውነት ተብሏል፤ ስብሃት ናፍቆናል፡፡
“…የሳቅ ጨዋታ የድሮው ያሁኑ ውሎዎች አሳልፈናል፡፡ የሱ ቢበልጥብኝም እኔ የማስቀውን ያህል ያስቀኛል፡፡ “እስቲ ጋሽ ስብሐት ብርቅዬ ገጠመኝህን ወርውርልን” እያልኩ እንዲያስደስተን እኮረኩረዋለሁ፡፡ …ጥሩ ጨዋታ እሚያጫውቱት ሰዎች አገናኘዋለሁ፡፡”
እንዲህ ያለው መስፍን ኃብተማርያም፤ ስብሃት ለእሱ ነግሮት ካሳቁት ቀልዶች አንዱንም አልነገረንም፤ ወይም መስፍን ለስብሃት ነግሮት ስብሃትን ያሳቁትን ቀልዶች አንዳቸውንም አልጻፈልንም፡፡ ኃይለጎርጊስ ማሞ ከዚህ በፊት ስብሃት ጽፏት አንብበናት የማናውቅ ስብሃት ያጫወተውን አንድ ምርጥ ቀልድ ጽፎልናል፤ ስቀናል፤ የይሁዲው እና የካቶሊኩ ቀልድ አንደኛ ደረጃ ቀልድ ናት፤ ሰቃይ ቀልድ ናት፡፡
“በውሎአችን ሁሉ ሞቅ ብሎን ጨዋታ ሳጫውተው፣ ጋሽ ስብሐት በውስጤ የተደበቀውን ወይም ተዳፍኖ የሚላወሰውን የተዋናይነት ፍቅር እያሰበ፣ ትክ ብሎ ያየኝና የሚያምሩ ጥርሶቹን ፍልቅልቅ አድርጎ “አሜሪካ ብትፈጠር ቶክ ሾው ላንተ ነበር” ይለኝ ነበር፡፡”
ኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት፤ አሁንም ለቶክ ሾው የአየር ሰዓት የሚሸጥ ይመስለናል፡፡
ደራሲ መሆኑ የማይቀረው ልጅ እና ስብሃት (ጌታቸው ወርቁ)
እከሌ ደራሲ ትሆናለህ ስለተባለ የሚኮን ነገር እንዳይደለ እናውቃለን፡፡ ጌታቸው ወርቁ ግን ከስብሃት ጋር ባሳለፋቸው ቆይታ ይህችን ነገር አይረሳትም፤ ጽፏት ለእኛም አድርሷታል፡፡
“አሁን መጨዋወት እንችላለን” አለኝ አይኑን ጨፍኖ፡፡ በወቅቱ በአእምሮዬ ላይ ይመላለስ የነበረውን አንድ ጥያቄ ወረወርኩለት፡፡ “አቦይ ለመሆኑ የተስፋዬ ገብረአብ ሥራዎችን የጋዜጠኛው ማስታወሻ እና የደራሲው ማስታወሻ አንብበሃቸዋል አልኩት፡፡”
“በሚገባ!”
“እንዴት አገኘኸው?” አልኩት፡፡
“አየህ አንተ እንግዲህ ወጣት ደራሲ መሆንህ ስለማይቀር (ይህቺ አባባሉ አንድ ጊዜም የአንባቢያን ጥያቄ በዓምዱ ላይ ሲመለስ “በጌቾ እድሜ ያላችሁ ወጣት አንባቢያን አንዳንዶቻችሁ ወጣት ደራሲ መሆናችሁ ስለማይቀር…” እያለ የሚፈጥረው ማነቃቂያ ናት) አስተውል፡፡ በአብዛኛው እውነት ከሀሰት ጋር ተጣምራ ነው የምትቀርበው፡፡ ተስፋዬም ይህቺን ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ አሪፍ ደራሲ ነዋ፡፡”
ጌቾ እንግዲህ ስብሃት እንደተነበየልህ፣ እንደበየነብህ ወይም እንደፈረደብህ የድርሰት ስራዎችህን እንደምታስነብበን እርግጠኛ ነን፡፡ እንዲህ ተባልኩ ያልከው እንደምትሆን ወይም እንደሆንክ አውቀህ ይመስለናል፡፡ ደራሲ መሆንህ አይቀርም ብሎሃል አይደል? ይቀር ይሆን እንዴ ብለን አንጨነቅም፡፡
አባቱ፣እሱ እና ስብሃት (አልአዛር ኬ.)
ስለእራስ በማተት በማተት፣ እዚህ መደበል ላይ የአላዛር ኬ “ስብሃት አባዬ እና እኔ” ከሁሉም ይልቃል፤ አንደኛ ነው፤ ይኸውላችሁ፡-
“ያደኩት አስራሁለት ወንድምና እህት የሆንን አባላት በነበርንበት ትልቅ ቤተሰብ ውስጥ ነበር፡፡ የመጀመሪያዎቹ አራት ታላላቆቻችን የእውነትም ታላላቆቻችን መሆናቸው በግልፅ ያስታውቅ ነበር፡፡ በተቀረነው መካከል የነበረው የእድሜ ልዩነት ግን ከሁለት አመት ያልዘለለ ስለሆነ ሁሌም በአንድ ላይ ሆነን የሚያዩን ሰዎች፣ ታላቁን ከታናሹ ለመለየት በጣም ይቸገሩ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡
አባታችን የቤተሰቡ ራስ ሲሆን እናታችን ደግሞ አባታችን ራስ ሆኖ የቆመበት ቤተሰብ ዋነኛ ምሰሶ ነበረች፡፡ መላው የቤተሰቡ አባላትም በዋናነት እናቴና አባቴ ያስፈፀሙት የሃይማኖታችንን ደንብ ስርዓትና ትዕዛዛት መሰረት ያደረገና ለረጅም ዘመን የዘለቀ ጠንካራና ጥብቅ የሆነ የእርስ በርስ ግንኙነት ነበረን፡፡ አብዛኞቻችን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከገባንበት ድረስ አንድም ጓደኛ እንኳ አልነበረንም፡፡ አንዳችን ለአንዳችን ወንድም ወይንም እህት ብቻ አልነበርንም፡፡ የምር ጓደኛሞችም ነበር፡፡ ከመካከላችን ለየት ያለው አባል አባታችን ነበር፡፡ እርሱ አባታችን ብቻ ሳይሆን እጅግ የቅርብ ጓደኛም ነበር፡፡ በተለይ ለእህቶቻችን የሚስጥር ጓዳቸው ነበር፡፡ በዚህ የተነሳም በዕለት ተዕለት ህይወታችን ውስጥ የምናደንቀውም ሆነ የምናነውረው ነገር በአብዛኛው ተመሳሳይ ነበር፡፡”
ከዚህ ቀጥሎ የዚህ አይነት አምስት ስድስት ሰባት … አንቀጾች ይቀጥላሉ፤ መጽሀፉ ላይ አሉላችሁ፡፡

ሞጋቹ ጠያቂ እና ስብሃት (ተሾመ ገብረስላሴ)
ይኸውላችሁ አሁን በረዥሙ ከምንጠቅሰው የተሾመ ገብረስላሴ ጽሁፍ ማን እና ምን ጎልቶ እንደወጣ ታዘቡ፡- “1992 ዓ.ም ክረምት ላይ ራስ መኮንን ድልድይ “ፋና ዴሞክራሲ አሳታሚ” (እፎይታ ጋዜጣ) ቢሮ የተስፋዬ ገብረአብ እንግዳ ሆኜ ስለዚህችው ስለኪነ ጥበብ እያወጋን እያለ በመሃል የጋሼ ስብሃት ስም ተነሳ፡፡ እንዲያውም ላስተዋውቃችሁ አለንና ጋሼ ስብሀት መቀመጫ ዘንድ ወሰደኝ፡፡ ጋሼ ስብሀት ኢንሳይክሎፒዲያ ያገላብጣል፡፡ ተዋወቁ አለን ተስፋዬ፡፡
“ጋሼ ስብሃት እጅግ ትሁት በሆነ እጅ መንሳት፣ እጁን ለሰላምታ እየዘረጋ “ስብሃት” አለኝ፡፡ ሳቄ ሊመጣ ነበር፤ ረስቶኛል፡፡
“ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ ልተዋወቅህ፤ ከአምስት ዓመት በፊት ይርጋለም ዶክተር አብርሃም አስተዋውቆን ነበር፡፡”
“አዎ አስታውሳለሁ፡፡ በጣም መጠየቅ የሚወድ ሞጋች ወጣት ገጥሞኝ ነበር፡፡ እርሱ ነኝ እንዳትለኝ!” አለ፤ ሶስታችም ተሳሳቅን፡፡
እርሱ በተካፈለበት “እፍታ” መጽሐፍ መድብል ውስጥ የኔም ጽሑፍ ስትካተት ደስታዬ ወሰን አልነበረውም፡፡
“ከአራት ዓመት በኋላ በድሉ ህንጻ ፊት ለፊት ካለው አሸናፊ መጽሐፍት መደብር ውስጥ ቁጭ ብሎ በአትኩሮት ሲያነብብ አገኘሁት፡፡ ያኔ እኔ ራዲዮ ፋና የኪነ ጥበብ ፕሮግራም አዘጋጅ ነበርኩ፡፡ በፕሮግራሙ አንድ አከራካሪ አጀንዳ ይነሳና ለሳምንታት፣ለወራት እያነጋገረ እንዲቀጥል የማድረግ አካሄድ እከተል ነበር፡፡ “ኪነጥበብ ለጥበብነቱ ወይስ ለማህበራዊ ፋይዳ?” የሚል አጀንዳ አንስቼ ብዙዎች ሙግት የገጠሙበት ጊዜ ስለነበር እርሱንም ላሳትፍው ጠየቅሁት፡፡
“ሙዱ” ጥሩ ስለነበር ቴፔን አውጥቼ በክርክርና ጥያቄ አጣደፍኩት፡፡
የሆነ ሰውዬ እና ስብሃት
“መልክዐ ስብሃት…” ላይ “ስብሃትን ከሌላ መዐዘን” የሚል ጽሁፍ አለ፡፡ የዚህ ሰው ጽሁፍ መነጋገሪያ ሆኗል፤ ሚልኪ ባሻ የሰውየውን ጽሁፍ “ዱልዱም ሰይፍ” ሲለው፣ ጠርጢዮስ “ባለሁለት ሰይፍ ጽሁፍ” ነው ብሎ ጽፏል፤ ከዚያ ለጥቆም ሚልኪ ባሻ በመልስ ጽሁፉ ተነስቶ ስብሃትን ለምን የጎሪጥ እንደሚያየው፤ አፍጥጦ አይቶት አሳየን፤ መልካም ሰው አባተ ደግሞ “ስብሃትን ከሌላ ማዕዘን” የሚለውን ጽሁፍ የጻፈው ሰውን ስብሃት ላይ አትንጠላል ብሎታል፡፡
የዚህ ስብሃት ወጣትነቴን አባከነብኝ የሚል ብኩን ጸሀፊ (እራሱ ነው ባከንኩኝ ያለው፣ አይዞህ አይባል ነገር¡)፣ስብሃትን ሰነፍ ጸሀፊ ነው ይላል፡፡ ኢዮብ ካሣ ደግሞ “በመልክዐ ስብሃት…” ገፅ 236 ላይ ያሰፈረውን መመልከት ይቻላል፤፡- “ለሥራው በነበረው ፍቅር (passion) እና ዲሲፕሊንም ቢሆን የተሻለ እንጂ ያነሰ አልነበረም፡፡ ጋሽ ስብሃት ከ10 በላይ መጻህፍትን ያበረከተልን ለጋዜጦች ወይም ለመጽሄቶች በሳምንት ይሁን በወር ከሚያቀርባቸው መጣጥፎች ጎን ለጎን ነበር፡፡ በአዲስ ዘመንም ሆነ በአዲስ አድማስ ጋዜጦች በአምደኝነት (colomunist) ሲሰራ ስራዎቹን በሰዓቱ ከማቅረብ የተስተጓጎለበት ጊዜ አልነበረም ወይም ስለማስተጓጎሉ ሲነገር አልተሰማም፡፡ ለምሳሌ በህይወት ዘመኑ ማገባደጃ ገደማ፣ በአዲስ አድማስ ላይ ሲፅፍ የሁለትና የሶስት ሳምንቶችን ፅሑፎች ቀደም አድርጎ ይልክ እንደነበር አውቃለሁ፡፡ ይሄ ዲሲፕሊኑ በሰራባቸው የህትመት ውጤቶች ዘንድ ሁሉ በግልፅ የሚነገርለት ሀቅ ነው፡፡ ክፋቱ ግን አክብሮት እና እውቅና ለማግኘት እንደተጨማሪ ነጥብ አልተቆጠረለትም፡፡ ፅድቁ ቀርቶብሽ በወጉ በኮነነሽ የሚለው ተረት እውን የሆነ ይመስላል…” በእርግጥ እውን ሆኗል እንላለን፡፡
ስብሃት ሰነፍ እንዳልሆነ ሌላም ምርቃት አለን፤ ጌታቸው ወርቁ ከፃፈው የምንዋሰው፣ መልክዐ ስብሃት ገፁ 80 ላይ ጌቾ (እንዲለው ስብሀት) እንዲህ ፅፏል፡- ያኔ በየሁለት ሳምንቱ ለንባብ በምትቀርበው ሮዝ መፅሔት ላይ ይፅፍ ስለነበር…. ይሁን እንጂ ነባር ፅሁፎቹ እንዳይደገሙ ከእድሜው ጋር በተያያዘ አልፎ አልፎ አመም የሚያደርገውን ሁሉ ችሎ አዲስ ለመፃፍ ሲታትር ላይ በእውነት እቀናበት ነበር፡፡ አይበቃም? ስብሃት ሰነፍ እንዳይደለ የሚናገር ሌላም ምስክር እንመርቅ፡፡ ምን ምን ላይ እንደፃፉት ባላውቅም አለማየሁ ገላጋይ የጻፉት ምስክር ናት፡- አለማየሁ ስብሃት ቤት ሲደርስ ስብሃት በአንድ እጁ ሀዱን ግጥም አርጎ ይዞ፣ በሌላ እጁ ብዕር ግጥም አድርጎ ይዞ ስቃይ ፊቱ ላይ እየተነበበ ይፅፋል
“ምን ሆነሀል?” አለማየሁ፡፡
“አሞኛል፡፡” ሰነፉ ሰውዬ፡፡
“እና ምን እያደረክ ነው?” አለማየሁ፡፡
“እየፃፍኩ፡፡” ሰነፉ ሰውዬ፡፡
“እንዲህ እያመመህ ምንድነው የምትፅፈው?” አለማየሁ፡፡
“ለዚህ ሳምንት የሚሆን ፅሁፍ፡፡” ሰነፉ ሰውዬ፡፡
“አሞሀል ፤ ለምን አትተወውም?” አለማየሁ፡፡
“አንተ ነህ እንዳመመን አይተህ ያወቅከው፤ አንባቢዎች በምን ሊያውቁ ይችላሉ?” (ወይስ አሞናል ብለን አዋጅ እናስነግር? ሳይል ይቀራል፡፡ አይልም አይባልም፡፡)
እና “ስብሃት ገብረእግዚአብሄርን ከሌላ ማዕዘን” በሚል የጻፈው እና ስብሃት “ሰነፍ እና ወጣትነቴን ያባከነብኝ ሰው ነው” የሚል ሰነፍ እና ብኩን ፀሀፊ፤ ስብሃትን ከወቀሰባቸው ጉዳዮች መሀል አንደኛው እንዲህ የሚል ንዑስ ርዕስ አለው፡- የአባት ጉርሻ፡፡ ከዚህ ስር የተፃፈውን እንጥቀስ፡-
“ከስብሐት ጋር ጥቂት ዘመናት ያሳለፍን ወጣቶች የስብሃትን “የአባት ጉርሻ” እናውቃለን፡፡ ዘነበ ወላ ስለዚህች ጉርሻ አጠራጣሪነት በማስታወሻ ላይ ሲመሰክር፡-
“በኔና በአብሮ አደጎቼ መካከል ያሳለፍነውን ህይወት በፈጠራ ጥበብ ተጠቅሜ የጻፍኩትን ሳነብለት ይደሰታል፡፡ አንዳንድ ቀንም “ልጅነትን አንብብልኝ እንጂ ይለኛል፤ የጠየቀኝን አደርጋለሁ፡፡ አንዴ አንዷን ምዕራፍ አንብቤ እንዳጠናቀቅሁለት ተነስቶ ቆመ፡፡ ወገቡን ይዞ ቁልቁል እያስተዋለ “ለዚህ መጽሐፍ እኔ ነኝ መግቢያውን የምጽፍልህ… Master Piece ወደ አማርኛ ስነጽሑፍ እየመጣች ነው” አለኝና ለሽንት ወጣ፡፡ … “በእንዲህ ባለ የአድናቆት ወቅት የማደምጠው አስር በመቶውን ያህል ብቻ ነው” ይለናል፡፡ ዘነበ ወላ ሲያብል ካልሆነ በስተቀር የስብሀትን አድናቆት አስር በመቶ ብቻ የሚወስድበት በቂ ምክንያት የለውም፡፡ ስብሐት ለርሱ አዋቂ ነው፡፡ ልባዊ ነው፡፡ ሽንገላና ውዳሴ ከንቱን የሚጠየፍ ነው፡፡ ታዲያ ስለ ዘነበ ወላ “ልጅነት” ያቀረበው ያድናቆት አስተያየት በምን ሰበብ ዘጠና በመቶ የሚወድቅ ሊሆን ይችላል? ስለዚህ ዘነበ ወላ ከዚያን ጊዜ ወዲህ ስለራሱ ያለው ግምት በስብሀት አስተያየት አልተነካም ቢለን ለማመን እንቸገራለን፡፡ ምክንያቱም ዘነበ በዚህ አባባሉ አንድም ስብሀት ይዋሻል፣ ይሸነግላል እያለን ነው፤ አንድም ደግሞ ከሥር ጀምሮ ስለስብሀት ልባዊነትና እውቀት ሲነግረን የመጣውን ሊያፈርሰው ነው ማለት ነው፡፡
የስብሃትን ጉርሻ በተመለከተ ሰዎችን በሶሰት መክፈል እንችላለን፤ አንድ፡- የስብሃትን ጉርሻ ለራሳቸው ያጎረሱ፡፡ ሁለት፡- ስብሃት ጉርሻውን ያጎረሳቸው፡፡
ሶስት፡- የስብሃት ጉርሻ እንዳማራቸው የቀሩ እና እጅጉን የተናደዱ፡፡እዚህ ጋር አንድ ያስተዋልነው ነገር ቢኖር፣ ፀሀፊው የስብሃትን ጉርሻ ያላገኘ ይመስላል፤ እናም ባለማግኘቱ በጣም የተናደደ እና የተቆጨ፤ እጅግ ስንጠራጠር ደግሞ፣ እጅግ በጣም የተናደደው እሱ እንዳለው ስብሀት ለሁሉም የሚያድለውን፡- “…ልባዊነት የማይነበብባቸው የግድ የለሽ አስተያየቶች…” ስላልደረሱት ይሆናል፡፡ ምስኪን!
አንድ የምታስቀኝ ነገር አለች፤ ዘነበ ወላ ማስታወሻ ላይ ጽፏት ያነበብኳት ናት፤ ዘነበ ወላ በደንብ ቢያስተውላት የሚጽፋት አይመስለኝም፡፡ የማስታወሻ ጽሁፍ ስራ እንዴት እንደተጠነሰሰ ነው የጻፈው፡፡ ስብሃት ዘነበን እንዲህ አለው፡-
“ሞትን እንቅደመው/እናሸንፈው እንዴ? ”አለ ስብሀት፡፡
“አዎ፡፡” አለ ዘነበ ወላ፡፡
“በል በቃ ስለኔ ጻፍ፡፡”
ማስታወሻ ተጻፈ፤ ያኔ ስብሃትም ዘነበም ሞትን ቀደሙት ወይም አሸነፉት፡፡ ስብሃት ስብሃትን ሆኖ፤ ዘነበ ስለስብሃት ጽፎ ሞት ተሸነፈ፡፡
ሌላም የምር የምታስቀኝ (የውሸት እስቃለሁ እንዴ?) አንድ ትርክት አለች፡፡ ስብሃትን ሁሌ አስፋልት የሚያሻግረውን ልጅ፡- “ሙሴያችን ነው፡፡” ብሎ ተሳልቆበታል፡፡ አለማየሁም የስብሃት ሙሴ ይሆን እንዴ? ዘመንን አሻግሮታል፡፡

 

Published in ጥበብ
Saturday, 31 August 2013 12:27

የባለ ቅኔ ቀን

ዓባይ ድልድዩ ስር...
ዓባይ እያጓራ - እየተፎገላ
ደም መሳይ ገላውን - ወርሶ ከአፈር ገላ
ሽልምልም እያለ - ከጣና ሲነጠል - ከጣና ሲከላ
ቁጭ ብዬ እያየሁ
እኔ እጠይቃለሁ
ከሀሳብ አድማሳት ሀሳብ አስሳለሁ
የባለቅኔ ቀን - የባለቅኔ አገር - ወዴት ናት እላለሁ፤
ይህ ሽበታም ድልድይ...
በጫንቃው መኪና - እንደተሸከመ
በጉያው ዓባይን - ሰርክ እንዳስተመመ
በቁር ሳይርድ ገላው - ሳይበድን አካሉ
የመጣን፣ የሄደን
እየተሸከመ - ሲያሳልፍ እያየሁ
በሸክሙ እደክማለሁ - በሸክሙ እዝላለሁ፤
እና እንዲህ እላለሁ
የልቡን እምቃት - እስትንፋሱን ሁላ - አልፎ ሂያጅ ለቀማው
እህ ባለ ጊዜ - ላጣ የሚሰማው
ከእንጉርጉሮው ዜማ - ሀሳብ ለመቀመር
ከሸክሙ ቅኔ ውስጥ - ትንሳኤ ለማብሰር
ሀሳብ አወጣለሁ
ሃሳብ አወርዳለሁ
ሀሳብ አስሳለሁ
የባለቅኔ ቀን - የባለቅኔ አገር - ወዴት ናት እላለሁ፤
‹‹ዓባይ ሽልምልሙ
ጣና ስልምልሙ
ድልድዩ ሽልሙ
አንድም ሳይጣሉ
አንድም ሳይስማሙ
እሾህ ያበቅላሉ
ዋርካ እያወደሙ፤››
ይላሉ ወፎቹ ከጣና ስርቻ - ከዓባይ በስተግርጌ - ዛፍ ላይ የሰፈሩት
የድልድዩን ቅኔ - በጣና ሙዚቃ - በዓባይ ሲቀምሩት፤
ይህን እያየሁ
ሀሳብ እጥላለሁ
ሀሳብ እሰቅላለሁ
ከሀሳብ አድማሳት
ሀሳብ አስሳለሁ
የባለቅኔ ቀን - የባለቅኔ አገር - ወዴት ናት እላለሁ፤
እላለሁ፤ እላለሁ
በቁጭት ሰበዜ
የህልሜን አክርማ ስፌት እሰፋለሁ፤
ስፌቱ ጣናዬ
ዓባይ አክርማዬ
ድልድዩ ሰበዜ የወፎቹ ዜማ - ወስፌ ነው መስፊያዬ - ስል እሞግታለሁ
በሀሳቤ ውጥን - ህዝብ እሰብዛለሁ - አገር እሰፋለሁ
ከመሸችው ጀንበር
ግራምጣ ሰግስጌ - ህዝብ አተልቃለሁ - አገር አልቃለሁ፤
ይህንን ከፍታ - ደግሜ አደምጣለሁ
ባሳብ ሰረገላ - እመነጠቃለሁ
ከዝምታ ስፌት - ህልም አስቀምጣለሁ፤
ከወፍ የተቀዳ - ከዓባይ የተሰማ - ከሀይቅ የተገኜ - ሙዚቃ እየሰማሁ
ድልድይ ስር ሆኜ - ዋርካ ተከልዬ - የባለቅኔ ህልም ልፈታ እጥራለሁ፤
አሁንም ያው አለሁ
ሀሳብ አወጣለሁ
ሀሳብ አወርዳለሁ
ከሀሳብ አድማሳት - ሀሳብ አስሳለሁ
ህልም እሚፈታባት
የባለቅኔ ቀን
የባለቅኔ አገር - ወዴት ናት እላለሁ፤
ታዲያ ሁላችሁም - በድንገት መጥታችሁ
ተነስ ካለህበት - ቤት ግባ ብላችሁ
ተውኝ አትቀስቅሱኝ
ካሳቤ አትመልሱኝ
ህልሜን አገሬ አውቃው - በአገሬ እስኪሰማ - በአገሬ እስኪነገር
ተውኝ ሳስስ ልኑር - የባለቅኔ ቀን - የባለቅኔ አገር!

Published in የግጥም ጥግ
Saturday, 31 August 2013 12:23

“ስሙኒዬን ኮሳት---”

ታክሲው እንዳወረዳቸው የቤታቸውን አቅጣጫ ትተው ወደ ማርያም ቤተክርሥቲያን በሚወስደው አስፋልት አቀኑ - ወይዘሮ ተዋቡ፡፡ ጭንቅላታቸው በሃሳብ ተወጥሯል፡፡ ሆስፒታል ውስጥ በጭንቀት ነው ያደሩት… በደም የጨቀየው ቀሚሳቸውን አልቀየሩትም፤ በነጠላቸው ሸፈኑት እንጂ… ዛሬ የ1995ዓ.ም.፣ የመጋቢት ወር የመጀመሪያ ሰኞ ነው፤ መጋቢት 21 ግን አይደለም፡፡ ካልተሳሳቱ የሚሄዱበትን ቤት ጧት ጧት ማርያምን ሊሳለሙ በሚመጡ ጊዜ ያዩት መስሏቸዋል፡፡ ‘እቺ ጭራቅ… እንዴት ልጇን አትፈልግም!... እባክሽ አንቺ ማርያም፣ እናቴ አማላጄ ከዚህ ጉድ አውጭኝ!’ እያሉ በልባቸው ይፀልያሉ፡፡
ተዋቡ፣ በላስቲክ የተገጠገጠው መንደር፣ በርቀት ታያቸው፡፡ ወደ አይጠየፍ ማርያም በሚወስደው የአስፋልት መንገድ ዳርና ዳሩ በሚገማሸሩ ትላልቅ ዛፎች ተሞሽሯል፡፡ በስተግራ በኩል በስርአት የተሰደሩት የላስቲክ ህንፃዎች፣ አካባቢውን የስደተኞች መጠለያ አስመስለውታል። ከእነዚህ የላስቲክ ህንፃዎች መካከል የትርፌን ቤት መለየት ፈተና የሆነባቸው ይመስላሉ…
“ከመለመን ይሻላል!... ልጆችሽንም አታንከራቻቸው… አይዞሽ ከሰራሽ ገንዘብ ታገኛለሽ። ልጆችሽም ያድጋሉ.. የኔን ብቻ ሳይሆን የድፍን መንበረ ፀሐይን ጠላ ሻጭ የጠላ ቂጣ እንድትጋግሪ፣ ጌሾውን እንድትወግጭ… አነጋጋርሻለ፡፡ አየሽ መለመን’ኮ የሚያሳፍር አጉል ልማድ ነው!” ብለው ማንም ሳያስታውሳቸው ከእኔ ቢጤዋ ትርፌ ጋር የተግባቡበትን ቀን እያማረሩ፣በአይናቸው አሁንም ቤቷን እየፈለጉ ነው… በፊት ለፊት የሚታያቸው የላስቲክ ቤት እንደነበረ ትዝ ይላቸዋል፡፡
‘አንቺም እኔን መቀመቅ ከተሽ… በርሽ ላይ ተጐልተሻል!... እንኳን ልጅ ምንም የጠፋባት አትመስልም… ለነገሩ አሁን ምን ልላት ነው!? ልጅሽ…’ ብለው ሳይጨርሱት በሃሳብ እየባዘኑ አይናቸውን ከትርፌ ላይ ተከሉ፡፡ አሁን ግን አንዳች ነገር እንደተፈጠረ አወቁ…
“እንዴ! አረ ወየው!...” አሉ ለራሳቸው - ማንም ግን አልሰማቸውም፡፡ መራመዳቸውን ትተው ቆሙ፡፡ ካለ ነገር ያ ህፃን በጨለማ እየተክለፈለፈ እንዳልመጣባቸው ተገነዘቡ፡፡
“አዎ! እናቲቱ አብዳ ነው!... ልትገለው ስትል ነው ከእኔ ቤት የመጣው! ትርፌ አበደች ማለት ነው!?... አረ!... አረ!... ገደለችው!...” አጉተመተሙ። በድርጊቱ ተገርመዋል፡፡ ስለማበዷም አምነዋል። ትርፌ በማረስመስ በሽታ የሚሰቃየውን የሦስት ዓመት ህፃን በአንድ እጇ፣ አንድ እጁን አንጠልጥላ ፈቀቅ አድርጋ ስትወረውረው ሰቀጠጣቸው። እንዳያናግሯትም ለራሳቸው ፈሩ፡፡ ካበደ ሰው ጋር ትግል መግጠም አይችሉ፤ የሚጠቅመው ወደ አንደኛ ፖሊስ ጣቢያ ሄደው ፖሊስ ማምጣት ነው፡፡ ትርፌ ሩጣ ከኋላቸው የምታንቃቸው ይመስል አስር ጊዜ እየዞሩ ወደ መጡበት ተመለሱ…
ትርፌ ህፃን ሲያለቅስባት መለኛ ናት፤ ማባበል ተክናበታለች… ሁለት ጊዜ ዝም እንዲል እንደ ጡሩንባ ታምባርቅበትና በሶስተኛው ዝም አልል ካለ በጥፊ ትለጋዋለች፡፡ የድሃ ልጅ ማጫወቻው፣ ማባበያው ይሄ ነው… በቃ… ልጅ መደብደብ፣ ማሰቃየት ጐጂ ልማድ እንደሆነ ማንም አልነገራት፤ ቢነግራትም አትሰማም፡፡ ከቡጢ ያልተናነሰ ጥፊ ያረፈበት ህፃን፣ የማልቀሻ ህዋሶቹ በለቅሶ ብዛት እስኪሰልሉ ድረስ እርር እያለ እያለቀሰ ነው፡፡ እሷ ግን የህፃኑን አይነ ምድር በያዘችው ጭራሮ ቆፈረችው… አይኗንም ከአይነ ምድሩ ሳትነቅል፣ “እንግዲህ ሙተህ እረፈውይ!... አንተ ሙትቻ!” ብላ ወስፋት የወጠረውን ሆዱን እንደ ከበሮ ጐሰም ጐሰም አደረገችው፡፡ ወዲያው መንጋጋውን በሃይል መልቅቃ ጉሮሮውን አየች… የፈለገችው አልታያትም። አንገቱን ወደታች ተጭና ማጅራቱን መታ መታ አደረገችው፡፡ ለሀጩ እየተዝረበረበ፣ አይነ ምድር ሲነካካ የቆየውን ጣቷን፣ወደ አፉ ከታ ጉሮሮው አካባቢ ዳሰሰች፣ ጣቷን ሳታወጣ ህፃኑ በትውኪያ ተጨነቀ፡፡ ትውኪያውን አፍጣ ብታየውም ምንም ነገር አላገኘችም…
“ዝም በል ስልህ አሰማይም!… አንተ ሙትቻ!... ካንተው ብሶ እልክ ደግሞ!...’እ’ በል!... ‘እ.እ’ በልህ አምጥይ!” ብላ ፊንጢጣውን አካባቢ እንደ ወፍጮ ቋት ጠበጠበችው፡፡ ቋቱ ባዶ በመሆኑ ፍጭ አላደረገም… የፊንጢጣውን ዳር ዳር በእጇ ጫን ጫን ካደረገች በኋላ፣ ሌባ ጣቷን በህፃኑ ፊንጢጣ ላከችና እንደወጥ አማሰለችው፡፡ ባእድ ነገር የተሰነቀረበት ህፃን፣ በዚህ ጊዜ ልሳኑ እስኪዘጋ ድረስ አምባረቀ፡፡ በርግጥ በለቅሶ ብዛት ሃይሉን ስለጨረሰ ጩኸቱ ቀንሷል፡፡
“እንግዲህ ሙተህ እረፈው… በቃ!... ያ መናጢ ገሎህ ሄደ!” እያለች የኔቢጤዋ ትርፌ በህፃኑ ላይ ተነጫነጨች… “ደሞ ልጅ ብሎ ነገር… አሞኝ ብልከው አይዴል… ያ ወደላ ጉድ የሰራኝ!... ቆይ!... የትም አድሮ አሁን እንዳመሉ ይመጣ የለ… እረግጠዋለሁ!” እያለች የማታውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናዋ እያየች ፉከራዋን ቀጠለች…
* * *
ትርፌ ሰሞኑን አሟት ስለነበር ከላስቲክ ቤቷ ኩርትም ብላ ነው የሰነበተችው፡፡ እንደሷ ግምት የህመሟ መንስኤ የጠላ ቂጣ መጋገሯ ነው። ለሷ የሚያዋጣት ሳይለፉ ቁጭ ብሎ መለመኑ ነው። “እጅግር እያለው ልመና ምንድን ነው!?... የሚያሳፍር መጥፎ ልማድ አይደል!” እያሉ እነ ተዋቡ እየጨቀጨቋት እንጂ መሥራቱን አትፈልገውም፡፡ ግን ለልጆቹም የሚበላውን እየሰጡ፣ አይዞሽ እያሉ እድሜ ለተዋቡ ሰርቶ መብላት እየለመደች ነበር…
ዛሬ እርሃቡም የልጆቹም ለቅሶ ሲብስባት፣ ወደ ማታ ለልመና ወደ መድሃኒያለም ቤተክርስቲያን አቀናች፡፡ እስከ ልጆቿ ቁጭ ብላ ስትለምን አመሸች። ሥራን የጠሉት እጆቿ ግን እንደ እስከዛሬው ብዙ ሳንቲም አላፈሱም፡፡ በለመኑት አንድ ብር ካሥር ሳንቲም ስኳር ድንች ገዝታ ልጆቿን ሸነጋግላ፣ እሷም ወደ አፏ አለች፡፡ የአምስት አመቱ የመጀመሪያ ልጇ ግን አንድ ሰውዬ የሰጡትን ሃያ አምስት ሳንቲም “አንጣ!” ብትለውም አልሰጣትም፡፡
“ክንዴ ስሙኒዊን አምጣትና ቡና ልግዛበት - እራሴን አሞኛል” አለችው፣ በዝችው በላስቲክ ቤቷ አንዳንድ ጊዜ ሞቅ ሲለው፣ ማታ ማታ ፍቅር የሚያጋራትን የቀን ሠራተኛ ወዳጇን እያሰበች፡፡
“እምቢየው!... ዲያቦ እገዣበታለው!” በማለት ሞገታት፡፡ እሷም ነገሩን ትታ የጐናቸውን ማረፊያ ማሰናዳት ጀመረች፡፡ የመደብ ላይ የወሲብ አጋሯ ዛሬ ድንገት ሊመጣ ስለሚችል ልጆቿን አስተኝታ መቆየት ይጠበቅባታል፡፡ ህፃን ክንዴ ግን እናቱ እንዳትሰማው በለሆሳስ፣ “እንካ ሻንቲምና ዲንች ስጠኝ” እያለ ትንሽ ወንድሙን ያባብሰዋል፡፡ ክንዴ ህፃኑ የፈረፈረውን ድንች ሲጠለቅም ጥርሱ ላይ እየቀረ ወስፋቱን ስላጮኸበት ሳያስበው በእጁ ከያዘው ላይም ቆረሰበት፡፡ ህፃኑ እንደ አንቡላንስ መኪና ሊጮህበት ሲያኮበኩብ ማታለያ ሳንቲሙን ሰጠው… ካለበለዚያ የወንድሙን ቀምቶ በመብላቱና በማስለቀሱ ከመሬት ጋር እንደምትቀላቅለው ያውቃል - ትርፌ ጋር ቀልድ የለም፡፡
ትንሹ ህፃን የተቀበላትን ሳንቲም ከድንቹ ጋር በድንገት ሲሰለቅጥ፣ “ኦዎ!...” ብሎ የማስመለስ ድምፅ አሰማ፡፡ ትርፌ ውልክሽ እያለች ስታየው ህፃኑ እየተናነቀው ነው፡፡ “አረ ይሄ ወዲያም!... ቀስ ብሎ አይበላም!...” ብላ ቀና ስታደርገው አይኑ ፈጦ ይተናነቀዋል፡፡ አንገቱን ወደ ላይ ቀና እያደረገች፣ “አንት እውር ሳንቲሙን ሰጠኸው እንዴ!...” ብላ ስታንባርቅበት ክንዴ ተብረከረከ፡፡ ህፃኑም እየጓጐረ ሳንቲሙን ወደ ከርሰ መቃብር ሲያወርዳት እናት ደነገጠች… በአፉ ምንም የሳንቲም ዘር የለም። ይልቁንም፣ ህፃኑ ምንም እንዳላየ ቁልጭልጭ ሲልባት ተጨነቀች፡፡
“ማን አባህ ስጥ አለህ!... እኔ አምጣ ብልህ እምቢ አላልክም!” ብላ ክንዴት በጥፊ ጆሮ ግንዱ ላይ ስታቀረናው መሬት ላይ ተዘረረ፡፡ ልትደግመው አንካሳ እግሯን እየጐተተች ስትጠጋው፣ ተነስቶ ነፍሴ አውጭኝ እያለቀ በጨለማው ፈረጠጠ፡፡ “አንት ሙትቻ! ቆይ… ትመጣ የለ!” ብላ ከላስቲክ ቤቷ በረንዳ ላይ ሁና ስትጮህበት፣ ጆሮ ግንዱን በእጁ ደግፎ እየተንሰቀሰቀ አስፋልቱን ይዞ ሮጠ፡፡
ክንዴ ጆሮውን እያሻሸ ትንሽ እንደሮጠ ቆመ። በጣም ይንሰቀሰቃል… በጥፊ የቀረናው ጆሮው ጭው ብሎበታል፡፡ አንዳች ነገር በጨለማው ውስጥ የመጣበት መሰለውና ደነገጠ፡፡ ድምፅ እያሰማ ማልቀሱን ተወ፡፡ ቀስ እያለ ወደዛችው ላስቲክ ቤት አመራ፡፡
ትርፌ የላስቲክ ቤቷን በር ዘግታ እየጮኸች ነው። ትንሹ ህፃንም ያለቅሳል፡፡ ከሁለተኛው የላስቲክ ቤት ያሉት የኔቢጤዎች መጥተው ስለተዋጠችው ስሙኒ ይንጫጫሉ፡፡ ክንዴ ወደ ቤቱ አጠገብ ሆኖ ሁሉንም ያዳምጣል፤ ቢገባ ምን እንደሚከተለው ያውቃል። ተጨነቀ፡፡ በጨለማው አይኑን ፍጥጥ ሲያደርግ፣ አንዳች ነገር ወደሱ እየመጣ መሰለው… ያቺ ትንሽ ልቡ በፍርሃት ቆፈን ተቀፈደደች፡፡ የእናቱ ንዴት እንዳልበረደላት ሲያውቅ ከቆመበት ተንቀሳቀሰ…
ክንዴ፣ “አባጅቦ እየመጡ ነው፣ ዝም ብላችሁ ተኙ… እርቦኛል ብሎ የሚያለቅስ ልጅ ካገኘ ጅቦ ይበላሉ…” እያለች ትርፌ ማታ ማታ እየራባቸው ሲያለቅሱ የምታስፈራራቸው ትዝ አለውና በፍርሃት እራደ፡፡ መምሸቱን እንጂ ከምሽቱ 3፡00 መሆኑን አያውቅም - በስኳር ድንች ተታሎ “ሙስና” የፈፀመው ረሃብተኛው ክንዴ፡፡
አሁን ትንሿ የክንዴ ጭንቅላት በሃሳብ ታጥራለች፡፡ የት እንደሚያድር እያሰበ ነው። ወደ እናቱ መሄድ አይታሰብም፤ እንደ ሙቀጫ ትወቅጠዋለች፡፡ ዘመድ አክስት አጐት የላቸውም፤ ወላጅ አባቱንም፣ እንኳን እሱ ትርፌም አታውቀው። ማታ ማታ ከዛች ላስቲክ ቤት እየመጣ ከእናቱ ጋር የሚላፋውን የቀን ሠራተኛ “አባቴ… ዳቦ….” ሲለው አይኑን እያጉረዘረዘበት መጥራቱን አቁሟል፡፡ እናም የት እንደሚያድር ጨነቀው…
ከደቂቃት በኋላ ያቺ ትንሽ ልቡ ሲብስባት መላ ፈጠረች፡፡ አዎ! ሲርበው የሚያጐርሱት፣ ሲጠማው የሚያጠጡት ተዋቡ ትዝ አሉት፡፡ ደስ አለው፡፡ ተዋቡ ቤት ደርሶ ሲገባ፣ “ለምን በጨለማ መጣህ?” ቢሉት ምን እንደሚል እያሰበ ወደ ጠላ ቤቱ አቀና። አሁን በርቀት የተዋቡ ቤት በር ገርበብ ብሎ እየታየው ነው… የጊቢው የሸንበቆ በራፍ ብትዘጋም ብዙ አላስጨነቀችውም፤ ገፋ ተደርጋ እንደምትከፈት ያውቃል፡፡
ምስኪኑ ክንዴ አሁን ከተዋቡ በር ላይ ደርሷል… የለመዳትን የሸንበቆ በር ገፋ ሲያደርጋት ግን እንደለመደው ሸተት አላለችለትም፡፡ እየደጋገመ እየገፋት እያለ ግን ታስሮ የሚውለው የጐረቤት ውሻ እየበረረ ከላዩ ላይ ተከመረበት፡፡ “ዋይ!” ብሎ ጩኸቱን ለቀቀው፡፡ የጠላቸውን ሂሳብ ከልጃቸው ጋር እያሰቡ፣ በትርፋቸው ማነስ ሲበሳጩ የነበሩት ተዋቡ፣ በር በርግደው ሲወጡ የጐረቤታቸው “መቻል” ከበራቸው ላይ ግዳይ ጥሎ አዩ፡፡
“መቻል!... አረ ሂድ!... የማነው ልጅ አረ!?” ተዋቡ የሚይዙትን የሚጨብጡትን አጡ፡፡ ጐረቤቱ እየተሯሯጠ መጣ፡፡ ህፃኑ በድንጋጤ ፀጥ አለ፡፡ “በጣም ተጐድቷል!... ቶሎ ሃኪም ቤት ይሂድ!...” አሉ፣ የተዋቡ ጐረቤቶች፡፡
“አረ በጣም ተጐድቷል!... ደም እየፈሰሰው ነው… ከማዘላችሁ በፊት በነጠላ ይታሰር…” ሁሉም በየፊናው ይጮኻል፡፡ የተዋቡ ልጅ፣ የተነከሰውን ህፃን አዝላ፣ ጐረቤት አስከትላ ሮጠች፡፡ ሙጋድ አካባቢ ያገኙትን ታክሲ ለምነው ወደ ሆስፒታል አመሩ፡፡ ክንዴ ሆስፒታል ገብቶ ሲታይ፣ ከእጁ የበለጠ ትከሻው ላይ ቦጭቆታል፡፡ ሀኪሞቹ እየተሯሯጡ አከሙት፡፡ መሰፋት ስላለበት አልጋ እንዲይዝ ተደረገ፡፡ ጐረቤቱ ሲመለስ ተዋቡ እስከ ልጃቸው ሆስፒታል አደሩ፡፡
ሀኪሞቹ “ውሻው ጤኛ ስለሆነ… ትንሽ ቁስሉ ያሰቃየው እንደሆነ እንጂ… ስለ ህይወቱ አያስቡ!...” ቢሏቸውም ተዋቡ ግን ይሄ ምስኪን ህፃን ወደ እሳቸው ቤት እየገባ ስለተነከሰ… እሳቸውን ባለእዳ አድርጐ እንዳይሞትባቸው ፈርተዋል፡፡ የእናቲቱ ልጇን አለመፈለግ ግን እንደ እግር እሳት እያንገበገባቸው ነው ያደሩት፡፡ ለዚህ ነው፣ በማለዳ የከረፋ ልብሳቸውን እንኳ ሳይቀይሩ፣ ጧት ከታክሲ እንደወረዱ በቀጥታ ወደ ትርፌ ቤት ያመሩት…
* * *
…ከትርፌ በር ላይ የሚያዩት ትእይንት የጤንነት አልመስላቸው ያሉት ተዋቡ፣ አሁን ካንደኛ ፖሊስ ጣቢያ አንድ ፖሊስ ይዘው ወደ ላስቲክ መንደሩ እያመሩ ነው፡፡
“አይዝዎ! እስዎን እኮ አያስጠይቅዎትም፣ በጨለማ እስዎ አላኩት… የገዛ እናቱ ትጠየቅ እንጂ!” ሲላቸው ፖሊሲ… ተዋበች፣ “የምልህን አልሰማኸኝም!... አብዳለች’ኮ ነው የምልህ… አየህ ትልቁ መሮጥ ስለቻለ ወደኔ መጣ… ያኛውን ህፃን ግን እንደ እባብ እየቀጠቀጠችው አይቼ!... በፊንጢጣው እንጨት፣ ጣቷን እየላከችበት ስልህ… አይ!... ትርፌማ አብዳለች… እሱማ ድህነቱስ ያሳብድ የለ!... ባይሆን ግን እሷ ሥራ ጠልታ ነው…” አሉ ተዋቡ፣ ምን እንዳሉ በወጉ ሳያጤኑ፡፡ ተዋቡ ልጁ ቢሞት ያስጠይቀኛል ብለው ፈርተዋል፡፡
“አየህ!... አረ እውልኝ… አሁንም አልተወችውም… ልትገለው ነው!”
“እህ!... እቺስ አመለኛ ናት! አንድ ጊዜ የማርያም እለት ጣቢያው ፊት ለፊት ቁጭ ብላ እየለመነች ሳለ እንደዚሁ ልጇን በድንጋይ መታው፣ አድምታው አስፈራርተን… ልጅ… የራስ ልጅም ቢሆን መደብደብ እንደማይገባ፣ ጐጂ ልማድ እንደሆነ አስተምረናት ነበር’ኮ” አለ ፖሊሱ፣ ያለፈውን ገጠመኝ እያስታወሰ።
“ዛሬማ አብዳለች’ኮ ነው የምልህ… አየህ… ቆይ ተመልከት… ቂጡን ምን እያደረገችው ነው ልጄ!?... ቆይማ እያት…” አሉ ተዋቡ ድምፃቸውን ቀንሰው በሹክሹክታ፡፡ ትርፌ የህፃኑን ፊንጢጣ መልግዛ አጐንብሳ እያየች ጣቷን ስትልከው፣ ይሄ መከረኛ ህፃን ድምፁ ሰልሎ ሲያላዝን አዩ… ፖሊሱ በሁኔታው ደነገጠና ፈንጠር ፈንጠር ብሎ በመራመድ፣ “አንቺ እብድ ልትገይው ነው!” አላት፡፡
ትርፌ ድንግጥ ብላ፣ “ምን ብዬ እኔ እገለዋለሁ!... ይሄ ሙትቻ እራሱ ሊሞት ነውይ… ለቡና መጠጫዬ ያልኳትንም…” እያለች ሳለ ንግግሯን አቋርጠው ተዋቡ፣ “ያኛውንም ልጅሽን በጨለማ አባረሽ ለጅብ አስበላሽው አንቺ ጨካኝ!” በማለት ጮኹባት፡፡
“ተነሽ ቀጥይ!... አውቆ አበድ!” በማለት ፖሊሱ ገላመጣት፡፡
“ደሞ በልጄ የፈለኩት ባረገውሳ!... ልታሰር ነው የምሄደው!” በማለት ትርፌ በተራዋ በሃይለ ቃል ተናገረች፡፡
“ልጅሽንስ ቢሆን ገለሽ ትቀመጭ መስሎሻል!... ‘እፀድቅ ብዬ ባዝላት…’ አሉ… ጦስሽ ለኔም ተረፈኝ!” አሉ ተዋቡ፣ ቁጣና ግርምት እየተቀላቀለባቸው፡፡
“ለዚህ ሁሉ የሚያበቃኝማ… ያ ዴንዴሳም ነው!” የቡና መግዣዬን ሰጥቶ…” አለች ትርፌ፣ ያዘለችውን ልጇን በትከሻዋ እያመናጨቀች፡፡
“አንቺ!... ቀስ አርጊው!... ማሳደግ የማትችይውን ከመውለድ መጀመሪያ ሰብሰብ አትይም ነበር… እንደ እባብ ቀጥቅጠሽ ከምትገያቸው!... ከዚህ በፊትም ተነግሮሻል!...” አለ ፖሊሱ በሁኔታዋ እየተበሳጨ፡፡
“አይ ተዋቡ! አውቆ አበድ ናት ብዬሁ የለ…”
“እህ!... አውቆ ይታበዲያል ደ’ሞ!?...” አለና ወደ ቢሮ ሳይገቡ በቁማቸው፣ ትርፌን በጥያቄ አዋከባት።
“ለመሆኑ በጨለማ ልጁን ለምን ከቤት አስወጣሽው!?”
“የቡና መግዣ ስሙኒዬን ሰጥቶ ይህን ሲያሳንቀው እሳ!”
“እና ምንም የማያውቀውን ህፃን በጨለማ ታባርሪያለሽ?... አንቺ ጨካኝ!”
“መች አባረርኩት፣ ገና በጥፊ ሥጋጋው ሩጦ ሄደ እንጂ…” እያለች ሳለ ጀርባው እንደ ወፍጮ ቋት ሲጠበጠብ፣ መላ አካሉ ሲጐረጐር አድሮ፣ ያረፈደው ህፃን ከእናቱ ትከሻ ላይ እያለ በድንገት ተቁነጠነጠ፡፡ ወዲያው ከጀርባዋ ወርዶ ጣቢያው በር ላይ ቁጢጥ አለ፡፡ የልጇ ነገረ-ሥራ ያላማራት ትርፌ፣ እንደ መብረቅ ብትጮህበትም፣ በህፃኑ ፊንጢጣ በኩል አንዳች ቆሻሻ አመለጠ፡፡
ትርፌ ቀልጠፍ ብላ ወደ ልጇ አይነምድር ስትጐነበስና ስንጥር ስታነሳ፣ ለጣቢያው ንፅህና በመጨነቋ ሁሉም በውስጣቸው አደነቋት፡፡ እሷ ግን ግዳይ ለመጣል አንደሚያደባ አስተዋይ አዳኝ አይኖቿን ተክላ፣ አይነምድሩን በስንጥሯ ደጋግማ ቆፈረችው… ወዲያው የሳንቲም ብልጭታ ከዓይነምድሩ ላይ ስታይ በስሜት፣ “እሰይ!... ስሙኒዬን ኮሳት…” በማለት ስትደመም፣ ከበዋት የነበሩት ሰዎች ሁሉ በሳቅ ተንከተከቱ… ድህነትም በተራው በሳቅ ተንከተከተ… ቂ.ቂቂቂ…

Published in ልብ-ወለድ
Saturday, 31 August 2013 12:23

ዘፍመሽ ግራንድ ሞል

“የስኬት ምስጢራችን ትጋትና ለችግር ያለመሸነፍ ነው”
አራት ሲኒማ ቤቶች አራት ሲኒማ ቤቶች
አንድ ፎቅ የቤተሰብ መዝናኛ

በአሁኑ ሰዓት በዓለም ግዙፍ የመገበያያ ሞሎች ባለቤት በመሆን ቻይናን የሚወዳደራት አልተገኘም፡፡ በ892ሺህ ካ.ሜ ወለል ላይ ያረፈው ትልቅ የገበያ ማዕከል በዓለም ቀዳሚ ነው፡፡ እዚያው ቻይና ውስጥ በ680ሺህ ካ.ሜ ወለል ላይ የሰፈረው የቤጂንግ ሞል በዓለም የሁለተኝነትን ደረጃ ይዟል። በ480ሺህ ካ.ሜ ወለል ላይ ያረፈው የፊሊፒንስ ሞል ሦስተኛ፣ በ465ሺህ ካ.ሜ ወለል ላይ የሰፈረው የማሌዥያ ሞል ደግሞ አራተኛ ነው፡፡ ቀደም ሲል ከ1986 -2004 ድረስ በዓለም 1ኛ የነበረው የካናዳው ዌስት ኤድመንተን ሞል፣ አሁን አራት ደረጃዎችን ተንሸራትቶ 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአገራችንም ትላልቅ የገበያ ማዕከላት ብቅ ብቅ እያሉ ነው፡፡ ለአብነት ደንበል ሲቲ ሞል፣ ጀሞ ሞልና ኤድና ሞልን… መጥቀስ ይቻላል፡፡ በቅርቡ ደግሞ መገናኛ አደባባይ አካባቢ በ4ሺ ካ.ሜ ወለል ላይ ያረፈው ዘፍመሽ ግራንድ ሞል በአገራችን የሞል ታሪክ አዲስ ነገር ይዤ መጥቼአለሁ ይላል፡፡ ስምንት መውጫና መውረጃ ተሽከርካሪ ደረጃዎች (ስካሌተርስ)፣ ሁለት ከውስጥም ከውጪም የሚያሳዩ የመጓጓዣ አሳንሰሮች (ሊፍት)፣ አንድ ግዙፍ የዕቃ ማጓጓዣ ሊፍት፣ 250 ሱቆች መያዛችን እንዲሁም በአንድ ጊዜ ከ1,200 ሰዎች በላይ የሚያስተናግዱ አራት ሲኒማ ቤቶች፣ 12 የተለያዩ አገራት ሬስቶራንቶች (food courts) ማካተታችን በአገራችን የመጀመሪያው ያደርገናል ይላሉ - የዘፍመሽ ግራንድ ሞል ሥራ አስኪያጅ አቶ ነጋ አስፈሃ፡፡
አቶ ነጋ፣ በአሜሪካ ለ22 ዓመት ከኖሩ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት ከሰባት ዓመት በፊት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአሜሪካ በማርኬቲንግ ማኔጅመንት አግኝተዋል። በሙያቸው በግል ድርጅቶች ውስጥ በመሥራት ሰፊ ልምድ ከማካበታቸውም በላይ ከቤተሰብ ጋር አነስተኛ ቢዝነስ አቋቁመው መርተዋል፡፡ አሜሪካ እያሉ ሞሎችን የማማከር ልምድ እንደነበራቸው የሚናገሩት አቶ ነጋ፤ ከአሜሪካ ጓዛቸውን ጠቅልለው ወደ አገራቸው ከተመለሱ አራትና አምስት ዓመት ሆኗቸዋል፡፡ እዚህ ከተመለሱ በኋላ ዘፍመሽ ግራንድ ሞልን በተለያየ ደረጃ ሲያማክሩ ቆይተው፣ ሥራ አስኪያጅ የሆ ኑት ከስድስት ወር በፊት እንደሆነ ገልፀዋል፡፡


ዘፍመሽ ግራንድ ሞልን አስመልክቶ ከአቶ ነጋ ጋር ያደረግነውን ቃለ - ምልልስ በዚህ መልኩ አቅርበናል፡፡ ለመሆኑ ሞል በአማርኛ እንዴት ይገለፃል? አልናቸው፡፡
ሞል በቀላል አነጋገር የመገበያያ ማዕከል ሊባል ይችላል፡፡ በዓለም ደረጃ ሞል ሲባል አንድ አማካይ ቦታ ሰብሰብ ባለመልኩ የተለያዩ የንግድ ዘርፎች ተሰብስበው አገልግሎት የሚሰጡበት የገበያ ማዕከል ነው፡፡ የሞል ባህል ከ10 እና ከ15 ዓመት ጀምሮ በአገራችንም እየተለመደ ነው፡፡
ሞል ከሌላው የገበያ ስፍራ የሚለየው ባህርይ አለው?
አዎ! አማካይ የሆነ ቦታ ተፈልጐ፣ የሚከፈት የንግድ ማዕከል ነው፡፡ በንጉሡ ዘመን፣ መርካቶ “አዳራሽ” የሚባል የንግድ ማዕከል ተከፍቶ ነበር፡፡ አሁንም ድረስ አለ፡፡ የሞል ሐሳብ፣ ድሮም በአገራችን የነበረ ሊሆን ይችላል፡፡ የአገር ባህል ጥበብ፣ ጫማ፣ ቦርሳ፣…የተለያዩ ዕቃዎችን የሚሸጡ ሰዎች አሉ። ስለዚህ ሞል የተለያዩ የመገልገያ ዕቃዎችን ምቹና ደህንነቱ በተጠበቀ ቦታ ቤተሰብ የሚገበያይበት ቦታ ማለት ነው፡፡ የተለያዩ አነስተኛ ሱቆች በተራራቀ ስፍራ ተበታትነው ከሚነግዱ፣ አንድ ቦታ ሰብሰብ ብለው ምርትና አገልግሎታቸውን ሲያቀርቡ፣ ሸማቹ ከውጣ ውረድና ከድካም ይድናል ማለት ነው፡፡ ይህ ለየት ያደርገዋል፡፡
ዘፍመሽ ምንድነው?
ዘፍመሽ ፒኤልሲ መሠረቱ የቤተሰብ ንግድ ነው፡፡ ዋና ባለአክሲዮኖች (ሼር ሆልደርስ) ሁለት ናቸው፡፡ ወ/ሮ ዘውዲቱ አህመድና አቶ መሐመድ አህመድ ናቸው፡፡ ሁለቱም ማኔጂንግ ዳይሬክተሮች ናቸው፡፡ ሁለቱ ዋነኛ ይሁኑ እንጂ ሌሎችም ሼር ያላቸው የቤተሰብ አባላት አሉ፡፡ እንግዲህ ዘፍመሽ የባለአክሲዮኖቹ ስም የመጀመሪያ ፊደል ተገጣጥሞ የተፈጠረ የቤተሰብ ቢዝነስ ነው ማለት ነው፡፡
ዘፍመሽ መቼና እንዴት ተጀመረ?
ዘፍመሽ ሲመሰረት እዚህ አልነበርኩም፡፡ ቢሆንም ሲነገር እንደሰማሁት ከ15 ዓመት በፊት ነው የተመሰረተው፡፡ የፋሽን ጨርቆችን (ልብሶች) ከውጭ በማምጣትና በመለስተኛ ዋጋ በመሸጥ ነበር የጀመረው፡፡ ከዚያም ሥራው ውጤታማ በመሆኑ በተለያዩ አካባቢዎች ሱቆች ከፍቶ መንቀሳቀስ ቀጠለ፡፡ በአንድ ወቅት ዘፍመሽ 20 ሱቆች ነበሩት። ስኬታማ እየሆነ ሲሄድ የንግድ ዘርፉን ወደ ኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች (ቲቪ፣ ፍሪጅ፣ የተለያዩ የመብራት ዓይነቶች…) በመለወጥ መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡ ከዚያም የስኬት ጐዳናው እያማረ ሲሄድ አሁንም የንግድ ዘርፉን በመለወጥ ወደ ፈርኒቸር ዘርፍ በመግባት፣ የቤትና የቢሮ ዕቃ ማቅረብ ጀመረ። በዘርፉ ከፍተኛ ጥራት ያለው ዕቃ ከሚያቀርቡ ድርጅቶች አንዱ ሆኗል፡፡ አሁን ገርጂ ጃክሮስ አካባቢ ትልቅ ሾው ሩም (ስቶር) አለው፡፡ ካለፈው አምስት ዓመት ጀምሮ ደግሞ ወደዚህ ግራንድ ሞል ግንባታ ገባ፡፡
ይህን ሞል ለመገንባት ምን አነሳሳቸው?
በንግዱ ምክንያት ዕቃ ለማምጣት በሚሄዱባቸው አገራት፡- በቻይና፣ በዐረብና በአፍሪካ አገራት ሲንቀሳቀሱ ትላልቅ ሞሎች ያያሉ። እኛስ ለምንድነው እንደቻይና፣ ዱባይ… ትላልቅና ዘመናዊ ሞል የማይኖረን የሚል ሐሳብ አደረባቸው። ያሰቡትን ተግባራዊ ለማድረግ ወሰኑና ዲዛይን አሰሩ፡፡ ለገበያ አማካይ የሆነ ቦታ ተፈልጐ ከመገናኛ ድልድይና ከዲያስፖራ አደባባይ መኻል ያለው ቦታ ተመርጦ ግንባታ ተጀመረ፡፡
ቦታው ምን ያህል ነው? በግዢ ነው? በምሪት?
በሊዝ ተገዝቶ ነው፡፡ ጠቅላላው የመሬቱ ስፋት 11ሺህ ካ.ሜ ሲሆን፣ ሞሉ ያረፈው 4ሺ ካ.ሜ ላይ ነው፡፡ ሞሉ መገበያያ ብቻ ሳይሆን ሰው ዕቃውን ሲያማርጥና ሲገዛ ቆይቶ ሲደክመው አረፍ ብሎ የሚመገብበትና የሚዝናናበት የመገበያያ ስፍራ ነው። ይህን ያደረግነው በማስፋፊያ ሳይሆን ገና ዲዛይኑ ሲሰራና ሕንፃው ሲገነባ ጀምሮ ለሞል ነው የተሰራው፡፡ ከሱቆችና ከመዝናኛ በስተቀር የቢሮ ክፍሎች የሉንም፡፡ ያለው ቢሮ የዘፍመሽ የአስተዳደር ቢሮና አስፈላጊ አገልግሎት የሚሰጡ የባንክና የፋርማሲ ቢሮ ብቻ ናቸው፡፡
ይህን ሞል በአገራችን ካሉ ሌሎች የመገበያያ ማዕከላት ለየት የሚያደርገው ነገር ምንድነው?
ሞሉ በቂ ብርሃንና የአየር ማስተንፈሻ አለው። ሱቆቹም ጣራቸው ረዣዥም ነው፡፡ ውስጥ ከተገባ በኋላ እንደልብ የሚያንቀሳቅሱ ኮሪደሮች፣ 8 ተንቀሳቃሽ ደረጃዎች (ስካሌተርስ)፣ ተሳፋሪው ሱቆቹንና አካባቢን እያየ፣ ከውጪም ሰዎች ተሳፋሪውን እያዩ የሚጓዝበት 2 የመስተዋት አሳንሰሮች (ሊፍቶች)፣ ግዙፍ የዕቃ ማጓጓዣ አሳንሰር አለን፡፡ በየመኻሉ በርካታ ደረጃዎችና መላለፊያዎች፣ በየፎቁ በርካታ የወንዶችና የሴቶች መፀዳጃ ቤቶች አሉ፡፡ እነዚህ ነገሮች ለየት ያደርጉናል ብለን እናምናለን፡፡
ሌላው ደግሞ እዚህ የሚመጣ ሰው የፈለገውን ነገር ማግኘት አለበት ብለን እናምናለን፡፡ 250 ሱቆች ሲኖሩ በ40 ዘርፎች የተሰማሩ ናቸው፡፡ ሽቶ፣ ጫማ፣ መኪና ማስዋቢያ፣ የስጦታ ዕቃዎች፣ መጻሕፍት፣ የወንዶችና የሴቶች ፋሽን፣ የኤሌክትሮኒክስ ዞን (የተለያዩ ሞባይሎች፣ ቴሌቪዥኖች፣ ካሜራዎች፣ የልጆች ልብስና መጫወቻ…) ብዙ ዘርፎች አሉ፡፡ ከእነዚህ ዘርፎች ሸማቹ የሚፈለገውን ያገኛል ማለት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ የሸማቹ ደህንነትና ምቾት የተጠበቀ ነው፡፡ በስውር ካሜራና በግልጽ ጥበቃ ደህንቱን እንከታተላለን፡፡
ሸማቹ አማራጭ (Choice) እንዲያገኝም አድርገናል፡፡ ለምሳሌ የአልባሳትን ዘርፍ ብናይ 50 ሱቆች አሉ፡፡ ከእነዚህ ሱቆች ሸማቹ በዋጋና በጥራት እንደአቅሙ የሚመቸውን መምረጥ ይችላል፡፡
ዋጋቸውስ እንዴት ነው?
ለምሳሌ ከ50 ሱቆች መካከል ጃኬት በ600 ብርና በ1500 የሚሸጡ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በእነዚህ ዋጋዎች መካከል ያለው ልዩነት ሰፊ ነው፡፡ ከ900 ብር እስከ 1000 ብር የሚሸጡ ሊኖሩ ይችላል፡፡ ስለዚህ ሸማቹ እንደአቅሙ መምረጥ ይችላል፡፡
ሌላው ልዩ የሚያደርገን የሲኒማ ማዕከላችን ነው፡፡ 250፣ 350ና 700 ሰዎች ማስተናገድ የሚችሉና ሰቨን ዲ ሲኒማ ቤቶች አሉን፡፡ 700 ሰው በሚያስተናግደው ትልቁ ሲኒማ ቤት ቪ አይ ፒ አለው፡፡ በአንድ ጊዜ በአራቱ ሲኒማ ቤቶች የተለያዩ ፊልሞች ስለሚቀርቡ፣ ተመልካቹ እንደፍላጐቱ የአገር ውስጥ ወይም የውጭ አገር ፊልም የመምረጥ ዕድል አለው፡፡
አንድ ሙሉ ፎቅ የቤተሰብ መዝናኛ ማዕከልም አለን፡፡ ፎቁ በሞላ፣ ከትናንሽ ሕፃናት እስከ ታዳጊዎች ያሉ ልጆች የሚዝናኑባቸው ዘመናዊ መጫወቻዎች ይኖሩታል፡፡ ስለዚህ እንደየ ዕድሜያቸውና ፍላጐታቸው መርጠው ይጫወታሉ ማለት ነው፡፡ ልጆቹን ይዘው የሚመጡ እናቶች የሚያርፉበትና ለሕፃናቱ ዳይፐር የሚቀይሩበትም ክፍል ተዘጋጅቷል፡፡
7ኛ ፎቅ ላይ ሆኖ አካባቢውን 360 ዲግሪ እያዩ የሚዝናኑባቸውና የሚመገቡባቸው የ12 አገራት ሬስቶራንቶች አሉ፡፡ በእነዚህ ሬስቶራንቶች የተለያየ አገር ምግቦችና ባህላዊ ምግቦች አማርጦ መመገብ ይቻላል፡፡ የአገራችን፣ የቻይና፣ የዐረብ፣ የሕንድ፣ …ምግቦች ይሰናዱባቸዋል፡፡
ዘፍመሽ መነሻ ካፒታሉ ምን ያህል ነበር
15 ዓመት ወደኋላ ሄጄ የተጀመረበትን ካፒታል ማስታወስ አልችልም፡፡ ነገር ግን በመለስተኛ ትንሽ ካፒታል እንደሆነ መናገር እችላለሁ፡፡ የሰውን ፍላጐት በማጥናት ያንን ትንሽ ካፒታል በአግባቡ በመጠቀም፣ አነስ ያሉ ሱቆችን በመከራየት፣ ቤተሰቡ በሙሉ በመሥራት ነው ለእዚህ ደረጃ የበቁት፡፡
የዘፍመሽ ግራንድ ሞል ግንባታ ምን ያህል ብር ፈጀ?
በጣም ብዙ ሚሊዮን ብር ነው፡፡ 4ሺ ካ.ሜ ላይ ሳይሆን 1,000 ካ.ሜ ላይ ያረፈ ሕንፃ እንኳ ብዙ ሚሊዮን ብር እንደሚፈጅ መገመት ይቻላል፡፡ ሕንፃውን ማቆም ሳይሆን ፊኒሺንጉ ቀላል አይደለም፡፡ በመጀመሪያው ምዕራፍ የተከፈቱት ሃይፐርማርኬቱ፣ ሱቆቹና የ400 መኪና ማቆሚያ ስፍራ ነው፡፡ እስከ 3ኛ ፎቅ ያሉትን 250 ሱቆች አደራጅተን ሥራ ጀምረዋል፡፡ ሲኒማ ቤቱ፣ የልጆች መጫወቻውና ፉድ ኮርቱ፣ 5ኛ ፎቅ ላይ የሚሠራው የባህል ማዕከል ጋለሪ እያዘጋጀን ነው፡፡ እነዚህን ከ6-8 ወራት ውስጥ ለመጨረስ እየሰራን ነው፡፡ የልጆች መጫወቻዎቹንና የሲኒማ ቤቶቹን ዕቃ ለመግዛት ጨረታ ወጥቷል፡፡ ወጪው ቀላል አይደለም፡፡ ምን ያህል እንደፈጀ የሚታወቀው እነዚህ ሥራዎች ሲጠናቀቁ ነው፡፡
ዘፍመሽ በሞሉ ውስጥ የራሱ ሱቆች አሉት?
ሱቆቹ በሙሉ ለነጋዴ የተከራዩ ናቸው፡፡ እኛ ሱቅ የለንም፡፡ ሲኒማ ቤቶቹ፣ የልጆች መጫወቻውና ሬስቶራንቶቹ ከፍተኛ ወጪ ስለሚጠይቁ እኛው እንመራቸዋለን፡፡
የዘፍመሽ የስኬት ምስጢር ምንድነው?
ጠንክሮ መሥራትና ለችግር ያለመሸነፍ ነው። ቤተሰቡ በሙሉ ኃይለኛ ሥራ ወዳድ ነው፡፡ ባለቤቶቹ ራሳቸው ይሰራሉ፡፡ ሌላው ደግሞ ቅንነትና ኅብረተሰቡ ምን ይፈልጋል? ብሎ በማጥናት በቀላል ዋጋ ሰው የሚፈልገውን ማቅረብ ነው፡፡ በጣም ሳይደክም የከበረ ባለሀብት ካለ ገንዘቡን ያገኘው በሌላ መንገድ ነው ማለት ነው፡፡ የዘፍመሽ የስኬት ምስጢር፣ ትጋት፣ ቁርጠኝነትና የገበያ ሁኔታን አጥንቶ ማቅረብ ናቸው፡፡
ለምን ያህል ሠራተኞች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል?
የተጀመሩት ሥራዎች በሙሉ ሲጠናቀቁ፣ 280 ያህል ሠራተኞች ይኖሩናል፡፡ አሁን ከ75-80 ሠራተኞች አሉን፡፡

 

 

ከእርግዝናና ከወሊድ ጋር በተያያዘ በየቀኑ 68፣ በየሰዓቱ 3 ሴቶች ህይወታቸው ያልፋል
በአገራችን ከእርግዝናና ከወሊድ ጋር በተያያዘ በየቀኑ 68 ሴቶች በየሰዓቱ ደግሞ 3 እናቶች ህይወታቸው ያልፋል፡፡ የአብዛኛው እናቶች ሞት ደግሞ የሚከሰተው በደም መፍሰስ፣ በተራዘመ ምጥና በከፍተኛ የደም ግፊት ሳቢያ ነው፡፡ ለዚህ ችግር ዋንኛው ምክንያትም የጤና ተቋም በአካባቢ አለመኖር፣ የትራንስፖርት ችግርና ህብረተሰቡ በጤና ተቋማት መውለድ እንደሚገባው በቂ ግንዛቤ አለመኖር መሆናቸውም ተጠቅሷል፡፡
                                          .=========.
ከምዕተ አመቱ ግቦች አንዱ የሆነውን የእናቶችና ህፃናት ሞት ለመቀነስ በየክልሉ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ እንደሆነ ቢነገርም ችግሩ ግን እምብዛም መሻሻሎችን አለማሳየቱንና በተያዩ ክልሎች ከእርግዝናና ከወሊድ ጋር በተያያዙ ችግሮች የሚሞቱ እናቶችና ህፃናት ቁጥር አለመቀነሱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በአገራችን በየአመቱ 2.8 ሚሊዮን እናቶች የሚያረግዙ ሲሆን ከእነዚህ እናቶች መካከል በሰለጠነ ባለሙያ ታግዘው የሚወልዱት 10% የሚሆኑት ብቻ ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ 90% የሚሆኑት እናቶች ዛሬም የሚወልዱት ያለማንም እርዳታ በቤታቸው ውስጥ ነው፡፡ በአገራችን ከእርግዝናና ከወሊድ ጋር በተያያዘ በየቀኑ 68 ሴቶች በየሰዓቱ ደግሞ 3 እናቶች ህይወታቸው ያልፋል፡፡ የአብዛኛው እናቶች ሞት ደግሞ የሚከሰተው በደም መፍሰስ፣ በተራዘመ ምጥና በከፍተኛ የደም ግፊት ሳቢያ ነው፡፡
ለዚህ ችግር ዋንኛው ምክንያትም የጤና ተቋም በአካባቢ አለመኖር፣ የትራንስፖርት ችግርና ህብረተሰቡ በጤና ተቋማት መውለድ እንደሚገባው በቂ ግንዛቤ አለመኖር መሆናቸውም ተጠቅሷል። እናቶች ወደ ጤና ተቋማት ሄደው በሰለጠኑ ባለሙያዎች እንዳይወልዱ ያደርጓቸዋል ከሚባሉት ጉዳዮች መካከል “ሶስቱ መዘግየቶች” እየተባሉ የሚገለፁት ዋንኞቹ ናቸው፡፡ ከእነዚህም መዘግየቶች መካከል የመጀመሪያው በምጥ የተያዘችው ሴት ወደ ጤና ጣቢያ (ጤና ተቋም) ለመሄድ በመወሰን ላይ የሚኖረው መዘግየት ነው፡፡ በምጥ ላይ ያለችው እናት ወደ ጤና ተቋማት ሄዳ እንድትገላገል ውሳኔ የሚተላለፈው በአብዛኛው በባል ወይም በባል ቤተሰቦች ይሆናል፡፡ ይህም ሴቲቱ በጊዜ ወደ ጤና ተቋማቱ እንዳትሄድ ያዘገያታል፡፡ ሁለተኛው መዘግየት የምንለው ደግሞ ከውሳኔው በኋላ እናቲቱን ወደ ጤና ተቋም ለማድረስ የሚወሰደው መዘግየት ነው፡፡ ይህ ደግሞ በትራንስፖርት አለመኖር፣ በመንገድ ችግር እና መሰል በሆኑ ምክንያቶች የሚፈጠረው መዘግየት ነው፡፡ ሶስተኛው መዘግየት እናቲቱ ጤና ጣቢያ ከደረሰች በኋላ የሚፈጠርና በጊዜውና በወቅቱ እርዳታ ማግኘት ባለመቻልዋ ምክንያት ለጉዳት የምትዳረግበት መዘግየት ነው፡፡ እነዚህ 3 መዘግየቶች በርካታ እናቶችን ያለ አግባብ እንድናጣቸው ምክንያት እየሆኑ ነው፡፡ እነዚህን ችግሮች ተቋቁመው እርጉዝ እናቶች በጤና ተቋማት ውስጥ እንዲወልዱ በተለያዩ መንገዶች ጥረት የሚያደርጉና ለውጥ እያመጡ ያሉ ቦታዎች ናቸው ከተባሉ አካባቢዎች ጥቂቶቹን ሰሞኑን ለማየት እድል አግኝቼ ነበር፡፡
ቦታው ከአዲስ አበባ በ620 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ስፍራው በትግራይ ክልል ውስጥ ማይጨው እየተባለ የሚጠራው አካባቢ ነው፡፡ ወደዚህ ስፍራ ለመምጣቴ ዋንኛው ምክንያቴ ደግሞ የተቀናጀ የቤተሰብ ጤና ፕሮግራም (IFHP) ከዩኤስ ኤይዲ (USAID) ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ፣ በትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በእናቶችና ህፃናት ጤና ዙሪያ እያከናወናቸው ያሉት ተግባራት ለማየት ነው። የተቀናጀ የቤተሰብ ጤና ፕሮግራም በአሜሪካው አለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት (USAID) የገንዘብ ድጋፍ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ ፕሮግራም ነው፡፡ ይህ ፕሮግራም በቤተሰብ እቅድ፣ በእናቶችና ህፃናት ጤና ዙሪያ፣ በኤችአይቪ ኤድስ፣ በስርዓተ ፆታ እና መሰል በሆኑ የጤና ዘርፎች ላይ ከተለያዩ ክልሎች ጋር በጋራ የሚሰራ ነው፡፡ ፕሮግራሙ በዋናነት በፓዝ ፋይንደር ኢትዮጵያና በGSI የተቀናጀ ድጋፍ በጋራ የሚሰራ ሲሆን በትግራይ፣ በአማራ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች፣ በኦሮሚያ፣ በቤንሻንጉልና በሶማሊያ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ በ301 ወረዳዎች ውስጥ ይንቀሳቀሳል፡፡ ፕሮግራሙ በሚሰራባቸው ክልሎች ውስጥ በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉና እንዴት እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ የሚከታተል የቴክኒክ አማካሪ ኮሚቴ በአገር አቀፍ ደረጃ አቋቁሞ በየሶስት ወሩ ስራዎቹ ባሉባቸው አካባቢዎች እየተዘዋወር ይጐበኛል፡፡
ወደ ስፍራው ያቀናውና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመንግሥት መ/ቤቶች የተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎች፣ የተቀናጀ የቤተሰብ ጤና ፕሮግራም የሥራ ኃላፊዎችና የ(USAID) ተወካዮችን ያካተተው ቡድን፤ ጉብኝቱን የጀመረው ከታሪካዊቷ የማይጨው ከተማ በ12 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው መስዋእቲ ጤና ጣቢያ ነው፡፡ ስፍራው ጣሊያን አገራችንን ወርራ አብዛኛውን የትግራይ ክልል በተቆጣጠረችበት ወቅት ከፍተኛ የሞት ሽረት ትግል ተካሂዶ ኢትዮጵያውያን አርበኞች ከፍተኛ መስዋእትነትን ከፍለው በርካታ ጣሊያኖች በመደምሰስ አካባቢውን ነፃ ያወጡበት ስፍራ በመሆኑ መስዋእቲ የሚል ስያሜ እንደተሰጠው ይነገራል፡፡ በአካባቢው ለአገራቸው ክብርና ነፃነት ሲሉ ህይወታቸውን ላሳለፉት ኢትዮጵያውያን የመታሰቢያ ሐውልትም ተሰርቶላቸዋል፡፡
የመስዋእቲ ጤና ጣቢያ ሰናይ፣ ስምረት፣ ተ/አያና፣ መሆኒ ለተባሉ ቀበሌዎች ጭምር አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ አካባቢው ለጉዞ እጅግ አስቸጋሪ የሆኑ ቀበሌዎችም የሚገኙበት ሲሆን በእነዚህ ስፍራዎች የሚኖሩ እርጉዝ እናቶችን ወደ ጤና ጣቢያው ለማምጣት የአካባቢው ወጣቶች እየተደራጁ የትራንስፖርት አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እርጉዝ እናቶች የወሊድ ጊዜያቸው ከመድረሱ በፊት ወደ ጤና ጣቢያው በመምጣት እስኪወልዱና ከወለዱም በኋላ እስኪጠነክሩ ድረስ የሚቆዩበት ቤት ይዘጋጅላቸዋል፡፡ ማህበረሰቡ “አንድ ጣሳ ለአንዲት እናት” በሚል መርህ እያዋጣ ለወላዷ ሴት ገንፎና አጥሚት እንዲዘጋጅላት ያደርጋል፡፡ በአንዳንድ ስፍራዎችም ከተለያዩ ድርጅቶች በሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ የዱቄት፣ የስኳርና የአልባሳት ድጋፍ እንዲሰጥ ይደርጋል፡፡ ይህ አሰራርም ወደ ጤና ጣቢያው በመምጣት የሚወልዱ እናቶችን ቁጥር ለመጨመር እንዳስቻላቸው በመስዋእቲ ጤና ጣቢያ ውስጥ ያገኘናቸው የጤና ባለሙያዎች ገልፀውልናል፡፡
በመኸን፣ በኩኩፍቶና በሰመር መለስ ጤና ጣቢያዎችም በተመሳሳይ መንገድ ወደ ጤና ተቋማት እየሄዱ የሚወልዱ እርጉዝ እናቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ተነግሮናል፡፡
በአካባቢው ባሉ አንዳንድ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ በመግባት ያነጋገርናቸው የአካባቢው ነዋሪዎች እንደነገሩንም፤ አሁን አሁን ወደ ጤና ተቋማት እየሄዱ መውለድና የህክምና እርዳታ ማግኘት የተለመደ ጉዳይ እየሆነ ነው፡፡ እርጉዝ ሚስቱን ወደ ጤና ተቋም በመውሰድ እንድትገላገል ያላደረገ አባወራ፤ በአካባቢው እንዲወገዝና እንዲገለል በማድረግ እናቶች በእርግዝናና በወሊድ ጊዜ ወደ ጤና ተቋማት እንዲሄዱ የመቀስቀሱን ስራ የአካባቢው የልማት ሠራዊትና የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች እየተገበሩት ያለ ጉዳይ መሆኑንም ነግረውናል፡፡ ጤና ጣቢያዎች ከእርግዝናና ከወሊድ አገልግሎት በተጨማሪ የፌስቱላ ችግር ያጋጠማቸው ሴቶች ህክምና እንዲያኙ በማድረግ ወደቀድሞ ጤንነታቸው የመመለስ ተግባሩንም እየከወነ ይገኛል። በመኸን ጤና ጣቢያ አግኝተን ያነጋገርናትና ቀድሞ የፌስቱላ ችግር ተጠቂ አሁን ደግሞ የፌስቱላ አምባሳደር በመሆን እየሰራች ያለችው ስንዳዮ ዳርጐ አንዷ ነች፡፡ የፓዝ ፋይንደር ኢትዮጵያ ተጠሪና የተቀናጀ የቤተሰብ ጤና ፕሮግራም ኃላፊ ዶ/ር መንግሥቱ አስናቀ እንደገለጹት ከ66 ሚ.ዶ በላይ ተመድቦለት በሚንቀሳቀሰው በዚህ ፕሮጀክት በእናቶችና ህፃናት ጤና፣ በሥርዓተ ፆታ፣ የማህፀን በር ቅድመ ካንሰር ምርመራ እና በወባ በሽታ ላይ እንደሚሰሩና የፌስቱላ ችግር የገጠማቸው ሴቶች ህክምና የሚያገኙበትንና ወደቤታቸው ተመልሰው የቀድሞ ህይወታቸውን የሚመሩበትን መንገድ እንደሚያመቻች ተናግረዋል።
የእናቶችንና ህፃናትን ሞት ለመቀነስ እየተከናወኑ ባሉት ዘርፈ ብዙ ተግባራት ከፍተኛ ለውጥ እየታየ መሆኑን የነገሩን የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ የዓለም ፀጋይ፤ መንግሥት ፕሮግራሞቹን የማስቀጠልና ለውጤታማነታቸው ድጋፍ የማድረግ ኃላፊነት አለበት ብለዋል፡፡ በክልሉ አሁንም በቤት ውስጥ የሚወልዱ እናቶች መኖራቸውንም ጠቁመው፣ በቤታቸውም ሆነ በጤና ተቋማት ውስጥ በሚወልዱበት ወቅት የሚሞቱ እናቶች እንዳሉም ገልፀዋል፡፡
የ2005 DHS (የሥነ ህዝብና ጤና ቅኝት) እንደሚያመለክተው ከአንድ መቶ ሺህ ወላድ እናቶች ውስጥ 673 የሚሆኑት ከወሊድ ጋር በተያያዙ ችግሮች ይህችን ዓለም ይሰናበታሉ፡፡ ይህ አሀዝ በ2011 በተደረገው የ DHS (የሥነህዝብና ጤና ቅኝት) ቁጥሩ ወደ 676 አሻቅቧል፡፡ የጥናቱ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት፤ አሀዙ በእናቶችና ህፃናት ሞት ላይ ይህንን ያህል የጐላ ለውጥ አለመታየቱንና ዛሬም በርካታ እናቶችና ህፃናት ከወሊድ ጋር በተያያዙ ችግሮች ህይወታቸው እያለፈ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሚያወጣቸው መረጃዎች በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሚታየው የእናቶችና ህፃናት ሞት ቁጥር መቀነስ እያሳየ ነው። ሚኒስትር መ/ቤቱ ከምዕተ አመቱ ግቦች መካከል የሚጠቀሰው የእናቶችና ሕፃናት ሞት መቀነስ ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነና አንዲትም እናት ከወሊድ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች መሞት የለባትም በሚል መሪ ቃል እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ በተደጋጋሚ ቢገለፅም፣ ዛሬም በርካታ እናቶች ከወሊድ ጋር ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች እየሞቱብን ነው።
የDHS ጥናቱን መሰረት ብናደርግ እንኳን አንዲትም እናት እየተባለ መፈክር በሚነገርባት አገር፣ ዛሬም ከ100ሺ እናቶች 676 ያህሉ ህይወት ለመስጠት ህይወታቸውን ያጣሉ፡፡ የእነዚህን እናቶች ሞት ለመታደግ ይረዳሉ ከሚባሉ ጉዳዮች መካከል የህክምና ተቋማት በሌሉባቸው ወይንም አገልግሎቱን ለማግኘት አስቸጋሪ በሆኑባቸው አካባቢዎቹ ተቋማቱ እንዲቋቋሙ ማድረግ፣ በሙያው የሰለጠኑ ባለሙያዎች በስፋት እንዲኖሩና ባለሙያዎቹ የሙያ ሥነምግባራቸውን ጠብቀው ለህብረተሰቡ ተገቢውን ግልጋሎት እንዲሰጡ ማድረግና አገልግሎቶቹ ለሁሉም ማህበረሰብ ተደራሽ የሚሆኑበትን መንገድ ማመቻቸት ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው። እናቶች ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ እንዲወልዱ በመቀስቀስ ብቻ (አገልግሎቶቹን ዝግጁ ሳያደርጉ) በእርግዝናና በወሊድ ሳቢያ የሚሞቱ እናቶችንና ህፃናትን መታደግ አይቻልምና !

Published in ዋናው ጤና

በኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር፤ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደርና የገንዘብ ሚኒስትር ከነበሩት አቶ ይልማ ደሬሳ የተወለዱት ወይዘሮ ሶፊያ ይልማ፤ ላለፉት 22 አመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ተሳትፈዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም ለሁለተኛ ጊዜ የኢዴፓ ምክትል ፕሬዚደንት ሆነው በመመረጥ ፓርቲውን እያገለገሉ ነው፡፡ በደርግ እጅግ የተጎዳሁ ነኝ የሚሉት ወይዘሮ ሶፍያ፤ ኢህአዴጐችን “ደርግን የጣሉ ጀግኖች” ብለው እንደተቀበሏቸው ጠቅሰው፤ወደ ፖለቲካ የገባሁትም እነዚህን ሰዎች ለማገዝ ነበር ይላሉ። “በኋላ ግን ተስፋ መቁረጥ መጣ” ባይ ናቸው። የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ኤልሳቤት እቁባይ፤ ከፖለቲከኛዋ ሶፊያ ይልማ ጋር ባደረገችው ቃለምልልስ፣ተስፋ ያስቆረጣቸውን ጉዳይ ጨምሮ በአጠቃላይ በአገሪቱ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙርያ አነጋግራቸዋለች፡፡

የአገራችን የምርጫ ሥርዓት በሚያሳዝን መልኩ እየተበላሸ ነው…
ኢዴፓ ቅንጅትን አፍርሷል የሚለውን ውንጀላ አይቀበሉትም …
ንጉሱ “ጀግና መሪ”፣ ደርግ “የጥፋት መልዕክተኛ”፣ ኢህአዴግስ?

ስለራስዎ ይንገሩኝ….
ተወልጄ ያደግሁት አዲስ አበባ ነው፡፡ በትንሽነቴ እንግሊዝ ትምህርት ቤት ነው መማር የጀመርኩት፡፡ በዘጠኝ አመቴ አባቴ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው በመሾማቸው እዚያም ተምሬአለሁ፡፡ አባቴ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ ኮከበ ፅባህ ትምህርት ቤት ትምህርቴን ቀጠልኩ። አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲም ገብቼ ተምሬያለሁ፡፡ ነገር ግን ትምህርቴን ሳልጨርስ ወደ ጀርመን ሄድኩ። ምዕራብ በርሊን ውስጥ የጋዜጠኝነት ትምህርት ተምሬ መጣሁ፡፡ ትምህርቴን ከጨረስኩ በኋላ የጋዜጠኝነት ሙያን ስለምወድ በጋዜጠኝነት መስራት ጀመርኩ፡፡
ስራው እንዴት ነበር?
ስጀምር ሪፖርተር ነበርኩ፡፡ መንገድ ለመንገድ እየሮጥኩ ዜና እሰራለሁ፡፡ ጫማ ጠራጊውም ባለሱቁም ያውቀኝ ነበር፡፡ ባለፍኩበት መንገድ ሁሉ ሶፊ እያሉ ይጠሩኝ ነበር፡፡ ሬዲዮ እያለሁ ወይዘሮ ሮማንን አውቃቸው ነበር፡፡ ከሳቸው ስር ስር እያልኩ ሙያዬን በተግባር አዳብሬያለሁ፡፡ በጣም የማደንቃቸው ጋዜጠኛ ነበሩ፡፡ ነገር ግን የኔ ፍቅር የህትመት ጋዜጠኝነት ላይ ስለነበር በወቅቱ የነበሩትን ባለስልጣኖች ተማፅኜ ወደ ሄራልድ ጋዜጣ ተዛወርኩ፡፡ እዛም ስጀምር ሪፖርተር ነበርኩ፡፡ በኋላ ላይ ሹመት አገኘሁና የሴቶች አምድ አዘጋጅ ሆንኩ፡፡ ከዛ በአጋጣሚ የጋዜጣውን ኤዲተር አገባሁ፡፡ አንድ መስሪያ ቤት ውስጥ አንድ ላይ መስራቱ አይመችም ብዬ እኔ ሥራ ቀየርኩ፡፡
በስራዎ ከባለስልጣናት ጋር ተጋጭተው ያውቃሉ?
የሚያጋጭ ስራ ሰርቼ አላውቅም፡፡ መንግስት ነኝ ብሎ የተቀመጠውን መንካት ወንጀል እንደሆነ አውቅ ነበር፡፡ እኔ ብዙ አደላ የነበረው ለማህበራዊ ጉዳዮች ነው፡፡ በጃንሆይ ጊዜ ብዙ ብሩክ ነገሮች ቢኖሩም ብዙ ጥሩ ያልሆኑ ነገሮችም ነበሩ፡፡ ጥሩ ካልሆኑት ውስጥ አንዱ የፕሬስ ነፃነት አለመኖር ነው፡፡
ከዚያስ የት መስራት ጀመሩ?
የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን መስሪያ ቤት ውስጥ በህዝብ ግንኙነት ቦታ ገባሁ፡፡ ረጅም አመት የሰራሁት ቴሌ ነው፡፡ ከዛ በኋላ ግን ስራውን ተውኩትና እቤቴ ቁጭ አልኩ፡፡ ከዛም ሲስተር ጀምበር ተፈራ ለሚሰሩት ትልቅ ፕሮጀክት ከሌሎች ጋር ተወዳድሬ እንድሰራ ጠየቁኝና እዛም የህዝብ ግንኙነት ሆኜ ለስምንት አመት ከሰራሁ በኋላ፣ ስራውን አቁሜ ቤቴ ቁጭ አልኩ፡፡
ወደ ፖለቲካ እንዴት ገቡ?
እኔ በደርግ መንግስት እጅግ የተጎዳሁ ሰው ነኝ። በልጅነት እድሜዬ ያገባሁት ያልኩሽ ባለቤቴ ደርግ ከገደላቸው “ስልሳዎቹ” አንዱ ነው፡፡ ተገኘ ተሻወርቅ ይባላል፡፡ ከመገደሉ በፊት ምክትል የማስታወቂያ ሚኒስትር ነበር፡፡ ከሱ ቀደም ብሎም አባቴ ታሰሩ። ታመው ለአንድ ሳምንት ያህል ሆስፒታል ከገቡ በኋላ እስር ቤት እንደሞቱ ቁጠሪው፤ ሞቱ፡፡ ከዛም እኔና እናቴ ታሰርን፡፡ እጅግ በጣም አስከፊ በሆነ ሁኔታ ነበር የታሰርነው፡፡ ጣሊያን በሰራው የድንጋይ ንጣፍ ላይ እየተኛን ክፉ ዘመን አሳለፍን። ስታሰር የመጀመሪያ ልጄ በጣም ትንሽ ነበር፡፡ እኔን ከመስሪያ ቤት ስለሆነ የወሰዱኝ ከትምህርት ቤት የሚመልሰው ሰው በማጣቱ፣ ከምሽቱ ሶስት ሰአት ነበር የተገኘው፡፡ ብዙ ችግሮች ላይ ወድቀን ነበር፡፡ ይሄ ቁስል ሆኖብኝ ስኖር ደርግ ወደቀ፡፡ እኔም በምችለው አቅም ለዚች አገር ፖለቲካ ውስጥ ገብቼ መስራት አለብኝ አልኩና በወቅቱ “ኢድሃቅ” የሚባለውን ድርጅት ተቀላቀልኩ፡፡ ወቅቱ ፓርቲዎች እንደ እንጉዳይ የፈሉበት ጊዜ ነበር፡፡ ብዙ ፓርቲዎች ነበሩ፡፡ ያንን አየንና ጠንካራ ለመሆን፣ ለምን ከጠንካራ ፓርቲ ጋር ውህደት አድርገን አንሰራም በሚል፣ በአቶ ልደቱ አያሌው ጋባዥነት “ኢድሃቅ” የወቅቱን “ኢዴአፓ” ተቀላቀለ፡፡ ከዛን ጊዜ ጀምሮ በፓርቲው ውስጥ እያገለገልኩ ነው፡፡
በምን ሀላፊነት?
አሁን ለሁለተኛ ጊዜ የኢዴፓ ምክትል ፕሬዚደንት ነኝ፡፡ በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች ፓርቲዬን እየወከልኩ እሄዳለሁ፡፡ ፓርቲያችንን አስተዋውቃለሁ፡፡ የኢዴፓ ጠንካራ ቡድን የሚገኘው እንግሊዝ አገር ነው፡፡
ምርጫ እየደረሰ ነው?
አዎ ኢዴፓ በመተዳደሪያ ደንቡ መሰረት በየሁለት አመቱ ጠቅላላ ጉባኤውን ያደርጋል። የስልጣን ማራዘምም ካለ ጠቅላላ ጉባኤው ይወስናል፡፡ በቅርቡም ጠቅላላ ጉባኤ ይኖራል፡፡ የስራ ዘመናቸውን የጨረሱ በምርጫ ለሚመጣው ያስረክባሉ፡፡ ይህ እንደ ፖለቲካ ባህል እንዲያዝ እንፈልጋለን፡፡ አንድ ሰው ምንም ያህል ብርቱ እና አዋቂ ቢሆን ከሱ ሌላ የለም ብሎ ማመን ትክክል አይደለም፡፡ በውስጣችን ብዙ ጠንካራ ሰዎች እንዳሉ ስለምናውቅ እድሉ ይሰጣል፡፡ ያለበለዚያ ፓርቲው በአንድ ሰው ብቻ የሚታወቅና የሚታይ ይሆናል። ፓርቲ ደግሞ የግለሰብ ሳይሆን ተስማምተው የሚሰሩ ሰዎች ስብስብ ነው፡፡
የፖለቲካ ጉዞው ምን ይመስላል?
የተቃዋሚው ፖለቲካ በየወቅቱ ይለያያል። አንዴ ጠንካራ ይሆናል፤ ሌላ ጊዜ ይዳከማል፡፡ ለዚህ ከመንግስት በኩል ያለው ተፅእኖ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል፡፡ ፖለቲካውን ከተቀላቀልኩ በኋላ ባሉት አመታት የሚያስደስቱም የሚያሳዝኑም ሁኔታዎችን አይቻለሁ፡፡ በጣም አስደሳች የነበረውና በኋላ ሳያምርበት ቀረ እንጂ አራት ፓርቲዎች ሆነው የመሰረቱት ቅንጅት ነው፡፡ ቅንጅት በኢትዮጵያ ህዝብ ትልቅ ተስፋ የተጣለበት ፤ ከህዝብ ትልቅ ፍቅር የተሰጠው ፓርቲ ነበር፡፡ ነገር ግን ያንን ይዞ አልቀጠለም፡፡ ነገሮች ከመበላሸታቸው ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ ሁኔታዎች በተለይ በኢዴፓ እና ኢዴፓ ውስጥ ባሉ ግለሰቦች ላይ ማነጣጠሩ ደግሞ እጅግ በጣም ፈታኙ ጉዳይ ነበር፡፡ ኢዴፓ የቅንጅት አፍራሽ ሆኖ ልደቱ አያሌው ላይ የተካሄደውን ዘመቻ ሳስበው፣ ሁልጊዜም እንቆቅልሽ የሚሆንብኝ የኢትዮጵያ ህዝብ ያንን መቀበሉ ነው፡፡ አፍሪካ ውስጥ በሀይል ከማመን ቀጥሎ ትልቁ በሽታ ስም ማጥፋት ነው፡፡ ከኔልሰን ማንዴላ በስተቀር ብዙዎቹ አፍሪካውያን ጀግኖች በተካሄዱባቸው የስም ማጥፋት ዘመቻዎች ነው ተጠልፈው እንዲወድቁ የተደረጉት፡፡ ያ ክፉ ጊዜ ለኢዴፓ የማይረሳ ነው፡፡
ኢዴፓ ቅንጅትን አላፈረሰም የሚሉባቸው ማስረጃዎች ምንድን ናቸው?
ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ በወቅቱ እውነታችንን እንናገር ብንል ማን ተቀብሎን! ቅንጅትን የመሰረቱት ፓርቲዎች ወደ ውህደቱ ለመሄድ ከምርጫ ቦርድ የተሰጣቸውን ሰርተፊኬት እና ማህተም መመለስ ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ ኢዴፓ በዛው ውህደቱ ሊካሄድ በታሰበበት ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤውን አድርጎ ነበር፡፡ ውህደቱን በተመለከተም ጠቅላላ ጉባኤው የወሰነው ውሳኔ ቅንጅቱ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ያልጠሩ ጉዳዮች እስኪጠሩ ድረስ የፓርቲው ሰርተፊኬት እና ማህተም እንዳይመለስ የሚል ነበር፡፡ ይህ ግን ከውህደቱ ሂደት ስለማያግደን እንቀጥል ተባለ፡፡ ከጠቅላላ ጉባኤው ውሳኔ በላይ መሆን እንደማይቻል ሁሉም እያወቁት፣ ውሳኔው በሌላ ተመንዝሮ ከአሉባልታ ጋር ተዳምሮ ዘመቻ ተከፈተብን፡፡ እውነት ሰሚ አጣች፡፡ ህዝቡም እንዴት ብሎ ሳይጠይቅ፤ ምንድን ነው የሆነው ብሎ ሳይመረምር ተቀበለው፡፡ አንዳንድ ጋዜጦችም እውነቱን ስሙ ብንላቸው “የእናንተ እውነት ጋዜጣ አያሸጥም” የሚል ምላሽ ሰጡን፡፡ በፖለቲካ ውስጥ ዋናው ነገር አለመቀደም ነው፡፡ እኛ ለተፈጠረው ነገር አልተዘጋጀንም ነበር፡፡ እነሱ ቀደሙን፡፡ በወቅቱ የቅንጅቱ ሁኔታም ችግር ላይ ስለነበር፣ ነገሮቹን የሚሸከም ይፈለግ ነበር፡፡ ስለዚህ ውድቀቱ ኢዴፓ እና በተለይ ልደቱ ላይ እንዲሆን ተደረገ፡፡ አሁን ድረስ የሚሞግቱኝ ሰዎች አሉ፡፡ ምን አይነት ስር የሰደደ ነገር ነው እላለሁ፡፡ እስቲ መከራከሪያችሁን ወይም እውነታችሁን ንገሩኝ ስል የለም፡፡ ለነገሩ የተወነጀልንበትን ጉዳይ እውነት አድርገነው ቢሆን ኖሮ ምንኛ በከበደን ነበር፡፡ ህዝቡ ሁኔታዎቹን በሂደት እያያቸው፣ ወደ ኢዴፓ እየተመለሰ ያለውም ለዛ ነው፡፡ በወቅቱ እንግዲህ አውቆ የተኛን መቀስቀስ ባይቻልም በብዙ መልኩ ብዙዎችን አሳዝኗል፡፡
ቀጣዩ አገራዊ ምርጫ እየደረሰ ነው፡፡ የኢዴፓ ዝግጅት ምን ይመስላል?
ምርጫ በዲሞክራሲ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ እምነታችን ስለሆነ በምርጫ ገብተን እንወዳደራለን። ምርጫዎቹ ላይ ያለውን ችግር ጊዜ ይፈታዋል። የምርጫ ሁኔታዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ በሚያሳዝን መልኩ እየተበላሹ ነው፡፡ ነገር ግን ራስን ማኩረፍ ካልሆነ በስተቀር ሳትሳተፊ ብትቀሪ ገደል ግቢ ነው የምትባይው እንጂ የሚመጣ ነገር የለም፡፡ በምርጫው ተሳትፈን እውነቱን ቆሞ መናገር ትልቅ ነገር ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ህዝብ አማራጭ ሆነን ምንግዜም እንቀጥላለን፡፡
በምርጫ እጩ ሆነው ያውቃሉ?
አዎ በ1993ቱ አገራዊ ምርጫ ቦሌ ክፍለከተማ ተወዳድሬ ነበር፡፡ ምርጫዎቹን ሳያቸው የመጀመሪያው ምርጫ ከኋለኞቹ የተሻለ ነበር ለማለት ያስደፍራል፡፡ ሰዉ ነቅቶ በቅቶ ነበር። መንግስት ያንን እየተሻሻለ የመጣ ባህል እንዲጎለብት አልፈቀደም፡፡ ህዝቡ የመምረጥ እና በፖለቲካ የመሳተፍ ስሜት የሚኖረው በመጠኑም ቢሆን ትክክለኛ ነገር አገኛለሁ ብሎ ሲያምን ነው። ያለበለዚያ ከቤቱ ምን ሊያደርግ ይወጣል? የሱን ፍላጎት እና የሰጠውን ምላሽ ለማወቅ 1997ትን መለስ ብሎ ማየት ነው፡፡
ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል?
እኛ ምንግዜም ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረን እንጥራለን፡፡ ሲሆን ሲሆን የህብረት ሁኔታ ቢፈጠርም በጣም ፈቃደኞች ነበርን፡፡ ግን የገጠመንን ስናይ፣ አልፎ አልፎ ባደረግናቸው ሙከራዎች ችግሮች ገጥመውናል፡፡ ወደ ውህደት ለመግባት መቸኮሉ ዋጋ ያስከፍላል፤ አስከፍሎናልም፡፡ ለመዋሃድ ቢያንስ በመሰረታዊ ነገሮች ላይ መመሳሰልና መግባባት ያስፈልጋል። ስለዚህ ከበፊት ልምዳችን በመነሳት ነገሮችን በጥንቃቄ ነው የምናየው፡፡ ዘው ብለን ስምምነት ውስጥ መግባት አንፈልግም፡፡
በሦስት መንግስታት ውስጥ አልፈዋል፡፡ ሶስቱን እንዴት ያይዋቸዋል?
የማወዳደር ሁኔታ ሊኖር አይችልም፡፡ በኔ አመለካከት ምናልባት ልጅነቴንም በሳቸው ዘመን ስላሳለፍኩ ይሆናል፡፡ ንጉሱ ጀግና መሪ ነበሩ፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ ላይ ያሉ ብዙ መሰረታዊ ነገሮችን ያስቀመጡ መሪ ናቸው፡፡ ሰው ናቸውና ስህተት አልነበራቸውም ማለት አይደለም፡፡ እንደ እግዚአብሄር እንቁጠራቸው፣ እንከን አይኑራቸው የሚለው ዝም ብሎ ሀሳብ ነው፡፡ እንደ ሰው የተሳሳቱት ነገር ሊኖር ይችላል፡፡ እውነት ለመናገር ስህተታቸው እጅግ የጎላ አይደለም፡፡ ሁሉ ነገር የሚዛን ጉዳይ ነው፡፡ ሚዛኑ የሚደፋው ወዴት ነው ያልሽ እንደሆነ ወደ ጥሩ ነገራቸው ነው ብዬ ነው የማምነው፡፡ እዚች አገር ላይ ጠንካራ የትምህርት፤ የጤና፤ የመንገድ መሰረት ያስቀመጡ ናቸው፡፡ የወታደር መንግስት ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በየትኛውም አለም ላይ በጅቶ አያውቅም፡፡ ግሪክን ያህል ዲሞክራሲያዊት አገር ያጠፋው ወታደራዊ አገዛዝ ነው፡፡ ላቲን አሜሪካንም ተመሳሳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያም የተለየ ነገር አልገጠማትም፤ ኢትዮጵያ አፈር ድሜ የጋጠችው በደርግ ነው፡፡ የተማሩ ሰዎች (ያለቁበት፣ ተስፋ የሰነቁ ወጣቶች በጠራራ ፀሀይ ተገድለው፣ መሬት ለመሬት የተጎተቱበት ዘመን ነው፡፡ ወደ ሚዛኑ ስመጣ ደርግ ምንም ሰራ ቢባል ጭካኔው ሁሉንም ነገር ያፈርሰዋል፡፡ ሰውን የሚጨርስ መንግስት ምንም ዋጋ የለውም። አገራቸውን በእጃቸውና በእግራቸው ያገለገሉ፣ ኢትዮጵያውያንን የገደለ ነው፡፡ በእኔ በኩል ደርግን የማየው እንደ መንግስት ሳይሆን እንደ “የጥፋት መልእክተኛ” ነው፡፡
የመንግስቱ ኃይለማርያምን መፅሀፍ አንብበዋል?
አላነበብኩም ማለት ፊደል ከቆጠረ ሰው የማይጠበቅ ቢሆንም አላነበብኩም!! ምክንያቱም እሱ ከውሸት ውጪ ምን ሊፅፍ ይችላል?!
ወደ ሶስተኛው መንግስት እንምጣ?...
የኢህአዴግ መንግስት ሲመጣ በኔ በኩል ትልቅ ተስፋ ነበረኝ፡፡ ደርግን የጣለ መንግስት ጀግና ነው ብዬ ነበር የተቀበልኳቸው፡፡ ወደ ፖለቲካ የገባሁበት ምክንያትም እነዚህን ሰዎች ለማገዝ ነበር፡፡ በሂደት ግን ተስፋ መቁረጥ መጣ፡፡ አሁንም የሚዛን ጉዳይ ነው። የሚያጠፉትን እያጠፉ፣ የሚያለሙትን ያለማሉ፡፡ እንደ ደርግ ሙሉ በሙሉ የጥፋት መልእክተኛ ብቻ አይደሉም፡፡ ጥፋቱ ምን ያህል ነው ስንል ፖለቲካው ላይ፣ የሰዎች መብት ላይ፣ ፍትህ ላይ ብዙ ደካማነት ይታይባቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ በጣም ያሳፍራል፡፡ ኢህአዴግ እነዚህን ነገሮች ለመለወጥ እድል የነበረው መንግስት ነው፡፡ አልተጠቀመበትም፡፡ ባለፉት ሀያ ሁለት አመታት ኢትዮጵያ አልተለወጠችም የሚል ካለም ጭፍንነት ነው፡፡ ብዙ ነገሮች ተለውጠዋል። ነገር ግን ለሰው ልጅ የቁሳቁስ ለውጥ ብቻ አያረካውም፡፡ ተስፋ ያስፈልገዋል፡፡ መብቱን ይጠይቃል፡፡ ፍትህ ይፈልጋል፡፡ አለአግባብ መነጠቅ እና መባረር ሊደርስበት አይገባም፡፡ ስለዚህ ሚዛኑ ላይ ሳስቀምጠው መሻሻሉን ያጨልመዋል፡፡
ወደኋላ ልመልስዎትና…ከአሜሪካ ስትመለሱ አገርዎ ላይ ምን ገጠምዎት? የባህል ግጭትና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ…
አባቴ በአምባሳደርነት የቆዩት ስምንት አመት ስለነበር፣ ከዛ ስንመለስ በሁለቱ አገሮች የባህል ልዩነት ምክንያት አንዳንድ ነገሮች አጋጥመውን ነበር። አሜሪካን አገር ምንም ያልሆኑ ነገሮች እኛ አገር በሌላ መልኩ የሚታዩባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡ እኛ ወላጆቻችን የተማሩ ስለነበሩ ነፃነትን አጣጥመን ነው ያደግነው፡፡ አባቴ የለንደን ዩኒቨርሲቲ ምሩቅ ነበሩ፡፡ እናቴም በጦርነቱ ምክንያት ትምህርቷ ተቋረጠ እንጂ የህክምና ተማሪ ነበረች፡፡ ብዙ ገፋ አድርጎ መሄድ ሳይጨመርበት፣ አሜሪካን አገር በአስራ አራት አመት የወንድ እና የሴት ጓደኝነት ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ እኛ አገር ደግሞ እንደዛ አይነት ባህል የለም፡፡ ለነገሩ እኛም የማያስቀይም እንደሆነ ብናውቅም በባህላችን የማይፈቀድ ነገር አናደርግም ነበር፡፡ አባባም አይፈቅዱም፡፡ እንደመጣን ግን እኛም በጓደኞቻችን ሁኔታ ደነገጥን፤ እነሱም በኛ ደነገጡ፡፡ የሩቅ ዘመዶቻችንም ምን ጉዶች መጡብን ብለውን ነበር፡፡ እንዳልኩሽ እኛ ቤት “Can I take your daughter to dinner?” (ልጅዎትን እራት ልጋብዛት?) የተለመደ ነው፡፡
በአባትዎ በአቶ ይልማ ደሬሳ ዙሪያ ብዙ ነገሮች ይባላሉ፡፡ ለምሳሌ የታህሳስ ግርግር ጊዜ እነ መንግስቱ ነዋይ ሲገደሉ አባትዎም “እቴጌ ታመዋልና ይምጡ” ተብለው ተጠርተው እንደነበርና እሳቸውም “እኔ የገንዘብ ሚኒስትር እንጂ ሀኪም አይደለሁም” በማለታቸው ከሞት እንደተረፉ ይነገራል፡፡ እውነት ነው?
ቀልድ ነው፡፡ በፖለቲካ ዙሪያ ብዙ ቀልዶች ይነገሩ የለ፡፡ አባባ እንደዚህ ጮሌ አፍ የላቸውም። እንዲህ እንኳን አይሉም፡፡ እውነትም ተጠርተው ነበር፡፡ በዛን ቀን በአጋጣሚ “ጌቶች” (ንጉሱ ለማለት ነው) ብራዚል ስለነበሩ፣ አልጋወራሽን አስፈቅደው ከእናቴ ጋር ወደ ጅማ ይሄዱ ነበር፡፡ አባቴ ምንም የጠረጠሩት ነገር የለም፡፡ ይፈለጋሉ ሲባሉ፣ “ኧረ እኔ መንገድ እየሄድኩ ነው” ብለው መለሱ፡፡
የደራሲ ስብሀት ገብረእግዚአብሄር ባለቤት የነበረችው ሀና ይልማ የእርስዎ እህት ናት፡፡ ከተፋቱ ረጅም ጊዜ ቢሆንም በህይወት እያለ ትጠያየቁ ነበር?
በሚገባ እንጠያየቅ ነበር እንጂ! ልጁ ከውጭ ሲመጣም ተገናኝተን ድሮ የምንሄድባቸው ቦታዎች በመሄድ አብረን እናሳልፍ ነበር፡፡

  • የአንድነት “ጥይት ተናጋሪ” በኢህአዴግ “የተገፋ” ነው ተባለ
  • ዶ/ር` መረራ የኢትዮጵያን ፖለቲካ የበላውን ቡዳ ይጠይቃሉ?

እናንተዬ፤ የሰሞኑን የፖለቲካ ድባብ እንዴት አገኛችሁት? (የአውራው ፓርቲና የተቃዋሚዎችን ማለቴ ነው!) ድንገት ሳናስበው ተሟሟቀ አይደል? (ዕድሜ ለፀረ - ሽብር ህጉ!) በእርግጥ ኢህአዴግና ተቃዋሚዎችም ምስጋና ይገባቸዋል (ልብ ስለገዙ!) እንዴ…ዋናውን ተመስጋኝ ዘነጋሁት እኮ! (ብራቮ ኢቴቪ!) እውነቴን ነው የምላችሁ…ባለፈው ሳምንት በኢቴቪ “የፀረ ሽብር ህጉና የፓርቲዎች አቋም” በሚል ርዕስ የተላለፈው ውይይት ተወዳጅ እንደነበር መረጃዎች ደርሰውኛል (ኤልፓ ግን አሻጥር ሰርቷል!)
በነገራችሁ ላይ ከ97 ምርጫ ወዲህ የታየ ትልቅ የዲሞክራሲ ጭላንጭል እኮ ነው (የሰይጣን ጆሮ አይስማብን!) ግን ደስ አይልም …ገዢው ፓርቲና ተቃዋሚዎች በትልቅ የአገር ጉዳይ (አዋጅ) ላይ ህዝብ ፊት ሲሟገቱ! (Live ባይሆንም አናማርርም)
አንድ ምስጢር ልንገራችሁ፡፡ ለኢህአዴግ እንዳትነግሩብኝ ታዲያ! (promise?) በጣም ጥሩ! ለአንድ ዓመት በጠ/ሚኒስትርነት የመሩን የተከበሩ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ገና ሥልጣን ሲይዙ አስረግጠው እንደተናገሩት “የመለስን ሌጋሲ” በእርግጥም እያስቀጠሉ ነው፡፡ ራዕያቸውንም እያሳኩ ነው፡፡ ይሄውላችሁ… ዝም ብሎ የካድሬ ዲስኩር እንይመስልብን መረጃና ማስረጃ እየጠቀስን ብናወጋስ… (እንደሰሞኑ የፓርቲዎች ውይይት!) በአንደኛ ደረጃ የሚጠቀሰው ምን መሰላችሁ? ጠ/ሚኒስትሩ በሙስና ላይ የወሰዱት ቁርጠኛ እርምጃ ነው፡፡ በአንድ ዓመት ብቻ ስንት ተጠርጣሪ ሙሰኛ እንደተያዘ እስቲ ቁጠሩት… (እኔማ መቶ ከደረስኩ በኋላ መቁጠሩን ትቼዋለሁ!) ጠ/ሚኒስትሩ የገቡትን ቃል የፈፀሙት በሙስናና በሙሰኞች ላይ ብቻ አይደለም፡፡ በፓርላማና በኢቴቪ ያየናቸው በጐ ለውጦችም የመለስን ሌጋሲ ለማስቀጠል በአቶ ኃ/ማርያም አስተዳደር የተከናወኑ ተግባራት አካል ናቸው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተቃዋሚዎች የጨዋታ ሜዳ (እነሱ ምህዳር ይሉታል!) እየሰፋ መምጣቱን ማንም ሊክደው አይችልም፡፡ (ከ97 ምርጫ ወዲህ ሜዳው ጠብቦ ነበር አልተባለም?) አንድነት ፓርቲ ብቻውን በአንድ ወር ያካሄደውን ሰልፍ ብቻ መቁጠር በቂ ነው፡፡ አንዳንድ የ”ከፋፍለህ ግዛ” ስትራቴጂ አቀንቃኞች ምን እንደሚሉ ታውቃላችሁ? እነዚህ ሁሉ በጐ ለውጦች ከኢህአዴግ ሳይሆን ከአዲሱ ጠ/ሚኒስትር የፈለቁ ናቸው ይላሉ (ከፋፋዮች በሏቸው!) እነዚህ ወገኖች ያልገባቸው አንድ ነገር አለ፡፡ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ሥልጣን እንደያዙ ከውጭ ጋዜጠኛ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ፣ ምን ራዕይ እንዳላቸው ተጠይቀው፤ የሳቸው ራዕይ የፓርቲያቸውን ራዕይ ማስፈፀም እንደሆነ በማያሻማ ቋንቋ ተናግረዋል፡፡ ስለዚህ ማናቸውም ለውጦች ከግለሰብ ሳይሆን ከፓርቲው እንደሚመነጩ ማወቅ ብልህነት ነው፡፡ (እኛ ከለውጡ እንጂ ከባለቤቱ ምን አለን?)
እስቲ አሁን ደሞ አንዲት ቁምነገር አዘል ቀልድ ጣል ላድርግላችሁ፡፡ (ዘና እንድትሉ እኮ ነው!)
ዶክተር ጌታቸው ቦሎዲያ የዩኒቨርስቲ የባዮ-ኬምስትሪ አስተማሪ ነበር፡፡ ተጨዋች፣ እንደልቡ የሚናገር፣ በህይወት ሳለ ለመንግሥት ባለስልጣናት ግድ የሌለው፣ በራሱና በእውቀቱ የሚተማመን ሳይንቲስት ነበር፡፡ (እንዲህ ያለ ምሁር እንደ ዳይኖሰር ጠፍቷል ልበል?) አንድ ጊዜ ከስድስት ኪሎ ወደ አራት ኪሎ ሲመጣ አንድ የስድስት ኪሎ ተማሪ ጭኖ (lift ሰጥቶ) ይመጣል፡፡ አራት ኪሎ ወደ ሳይንስ ኮሌጅ እየተቃረቡ ሲመጡ ተማሪውን እንዲህ ሲል ጠየቀው፡፡ ዶ/ር ጌታቸው ወንድንም ቢሆን አንቺ ማለት ይቀናዋል፡፡
“የት ነው የምትማሪው?”
ተማሪው - ስድስት ኪሎ
ቦሎዲያ - ስንተኛ ዓመት ነሽ?
ተማሪው - አራተኛ ዓመት፤ ዘንድሮ እጨርሳለሁ
ሳይንስ ኮሌጅ አጠገብ አቁሞ እያወረደው፡
ቦሎዲያ - ቆይ ቆይ፤ ምንድነው የምታጠኚው ለመሆኑ?
ተማሪው - ፖለቲካል ሳይንስ
ቦሎዲያ - በይ በይ፤ ሳይንሱን ለእኔ ተይና ፖለቲካሽን ይዘሽ ውረጂ! (ምንጭ - አዲስ አድማስ)
ምሁሩ እኮ እውነታቸውን ነው፡፡ ፖለቲካ ብሎ ሳይንስ እኮ የለም - በተለይ በጦቢያ ምድር! ፖለቲካ እኮ እኛ አገር ሃሜትና አሉባልታ ነው፡፡ ፖለቲካ እኮ እኛ አገር ጠብና መጠላለፍ ነው፡፡ ፖለቲካ እኮ እኛ አገር የቀውስና የጥርጣሬ ምንጭ ነው፡፡ ፖለቲካ እኮ እኛ አገር መካካድና መዘላለፍ ነው፡፡
በነገራችሁ ላይ የመድረክ አመራር አባል የሆኑት ዶ/ር መረራ ጉዲና፤ “የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምስቅልቅ ጉዞና የህይወቴ ትዝታዎች” በሚል ርእስ በቅርቡ ለንባብ ያበቁት ጉደኛ መጽሐፍ አላቸው፡፡ እናላችሁ… መፅሃፉን ብታነቡት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶች መመደብ እንዳለበት ትገነዘባላችሁ፡፡ (ዶ/ር መረራ ከተቃዋሚ ፓርቲ አመራርነታቸው በተጨማሪም የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ናቸው፡፡) በመፅሃፋቸው ጀርባ ላይ ስለ ዶ/ር መረራ የፖለቲካ ህይወት የቀረበው አጭር መረጃ እንዲህ ይላል ፡- “በፖለቲካው ዓለም፤ ከ1960ዎቹ የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ እስከ ዛሬ በዘለቀው የኢትዮጵያ ሕዝቦች የመብት ትግል ውስጥ በመሳተፍ ሦስት መንግሥታትን ታግሏል፡፡ በደርግ ዘመን ለሰባት ዓመታት የፖለቲካ እስረኛ ሲሆን፣ ከ1997 እስከ 2002 የሀገሪቱ ፓርላማ አባል ነበር፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ኮንግረስና የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ የሚባሉ ድርጅቶችንና የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ህብረትና መድረክ የሚባሉ ጥምረቶች በሊቀመንበርነት መርቷል”
አያችሁልኝ… ፖለቲካ በእኛ አገር ሙያ (career) ሳይሆን ትግል ነው - ሲከፋ ለሞትና ለዝንተዓለም እስር ይዳርጋል፡፡ ካልከፋ ደግሞ ከአገር ያሰድዳል (ስደት እኮ ሰፊ ወህኒ ቤት ነው!) ዛሬ እንደው ላጓጓችሁ ብዬ እንጂ የዶ/ር መረራን መፅሃፍ የመቃኘት ዓላማ የለኝም፡፡ እንጂማ ስንት አጀብ የሚያሰኙ ታሪኮችና ገጠመኞችን እንደያዘ አልነገራችሁም፡፡ ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ፡፡ በባዶ ከምንለያይ ግን እስቲ አንዲት ነገር ከመጽሐፉ ላጋራችሁ፡፡ የኢትዮጵያዋና ችግሮች ሦስት ናቸው ይላሉ - ምሁሩ፡፡ አንደኛው - የትግራይ ልሂቃን “ስልጣን ወይም ሞት” ብለው ሥልጣንን የሙጥኝ ማለታቸው (የአባታቸው ርስት አደረጉት ለማለት ይመስላል)፣ ሁለተኛው - የአማራው ልሂቃን የኢትዮጵያዊነት ሰርተፊኬት (ሊቼንሳ) ሰጪ ነን ባይነት (የዜግነት ብቃትና ደረጃ አውጪ ማን አደረጋቸው ማለታቸው ነው) ሦስተኛው - የኦሮሞ ልሂቃን ብዙ ህዝብ ይዞ ልገንጠል ማለት (ግንድ እንዴት ይገነጠላል እያሉ ነው!)… እነዚህ ሦስት ጉዳዮች ካልተለወጡ አደጋው ይቀጥላል ባይ ናቸው - ዶ/ር መረራ፡፡ (የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ስለሆኑ እመኗቸው!)
የቀድሞው የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንትና የአሁኑ የአንድነት ፓርቲ ሊ/መንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ስለመፅሃፉ በሰጡት አስተያየት፤ “ዶ/ር መረራ ጉዲና የኦሮሞ ህዝብ የመብት ትግል ከተቀሩት የኢትዮጵያ ህዝቦች የመብት ትግል ጋር በማቀናጀት ሰፊ ሚና በመጫወት ላይ የሚገኝ ታጋይ ምሁር ነው፡፡ በህዝቦች እኩልነት ላይ የተመሰረተች ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንድትፈጠር የሚመኝ ሁሉ ሊያነበው የሚገባ መፅሃፍ ነው” ብለዋል፡፡ ከዶ/ር ነጋሶ ሃሳብ ጋር እስማማለሁ፡፡ ግን የምጨምረውም አለኝ፡፡ ከ1960ዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ጀምሮ እስከዛሬ የዘለቀውን የጦቢያ የመጠላለፍ ፖለቲካ ፍንትው አድርጐ የሚያሳይም መጽሐፍ መሆኑን ልገልጽላችሁ እወዳለሁ፡፡
በዚያ ላይ ዶ/ር መረራ አዋዝተው ስለፃፉት በእርግጥም መነበብ ያለበት የፖለቲካ መፅሃፍ ነው ባይ ነኝ፡፡ (ኮሚሽን የተከፈለኝ እንዳይመስላችሁ!) አንድ የገረመኝ የዶ/ር መረራ አባባል አለ - መጽሐፋቸው መጨረሻ ላይ፡፡ “የኢትዮጵያ ፖለቲካ ቡዳ ማነው” ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ (ፖለቲካ ሳይንስ አይደለም አላልኳችሁም!)
እኔ የምላችሁ… ባለፈው ረቡዕ ማታ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን በኢቴቪ የሰጠውን መግለጫ ሰምታችኋል? “አገልግሎቴን አሻሽያለሁ” እኮ ነው ያለን! ባለፈው ሳምንት በመብራት መቋረጥ የተነሳ በኢቴቪ የተላለፈውን የፀረ ሽብር ውይይት አልተከታተልንም ለሚሉ ዜጐች ምላሹ ምን ይሆን? እኔማ ለእነዚህ ተበዳዮች የፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻ ጀምሬአለሁ - ኤልፓን ለመክሰስ፡፡ (እኔ እንደ “አንድነት” ሚሊዮን ድምጽ አልፈልግም፤ 100 ይበቃኛል!) አንዲት ወዳጄ ስለ “ኤልፓ” ተነስቶ (ስለእሱ ሳይነሱ ውሎ ማደር እኮ አልተቻለም!) ያወጋችኝን ላካፍላችሁ፡፡
“ልጄ አፏን የፈታችው በምን እንደሆነ ታውቃለህ?”
“በምንድነው?”
ያው “አባ፣ እሚ” በሚለው መስሎኝ ነበር፡
“በራ… ጠፋ… በሚሉት ቃላት ነው”
(አይገርምም!)
ገባችሁ አይደል… መብራቱ አስሬ እየጠፋ ሲመጣ “በራ ጠፋ” እያለች አፏን ፈታች ማለቷ እኮ ነው፡፡ ይሄ መቼም አሳዛኝ ክስተት ነው አይደል? ምናልባት ኤልፓ በዚህ መልኩ መገለፁ “ያኮራኛል!” ሊለን ይችላል፡፡ (ይኩራ፤ መብቱ ነው!) ለእኛ ግን “አገልግሎቴን አሻሽያለሁ” የሚለውን “የአንደበት ግልጋሎቱን” (ከሰሞኑ የኢህአዴግ ሹመኛ ንግግር ቃል በቃል የቀዳሁት ነው!) ይተወንና መብራቱን እንደድሮው በፈረቃ ያድርግልን! ሰሞኑን ካመለጠን የፓርቲዎች ውይይት በተጨማሪ በመብራት ድንገተኛ መቋረጥ በየቤታችን የተቃጠለውን ቲቪ፣ ሬዲዮና ሌሎች ቁሳቁሶች “ሆድ ይፍጀው” ብለናል፡፡ (የፒቲሺን ዘመቻው እስኪጠናቀቅ!)
ባለፈው ሳምንት በዚሁ ጋዜጣ ላይ የወጣውን “የኢንጂነር ሃይሉ ሻውልና የኖርዌይ ኤምባሲ ውዝግብ” የተመለከተ ዜና አንብባችኋል? ለብዙ አመታት መኢአድን በሊ/መንበርነት የመሩት ኢንጂነሩ፤ የፓርቲያቸውን የእርስ በርስ ፉክቻ ተገላገልኩ ሲሉ የኤምባሲ ንትርክ ደግሞ ገጠማቸው፡፡ (የአገራቸውን ጉዳይ ሲገላገሉ የቤታቸው ጠበቃቸው!) እኔ ግን ስጠረጥር ኤምባሲው ኢንጂነሩን በደንብ ያወቃቸው አልመሰለኝም፡፡ እንዴ…ያፈነገጡ የመኢአድ አመራሮችን ተጋትረው ሲበቃቸው ሲሉ እኮ ነው ከፖለቲካ ጡረታ የወጡት፡፡ (ውዝግብ ብርቃቸው አይደለም ለማለት ነው!) “በፀባይ ቤቴን ካለቀቁ ከጐን አጥሩን አፍርሼ እገባለሁ” ያሉት ነገር ግን አልተመቸኝም፡፡ ኤምባሲ ማለት አገር ማለት ነው ይባል የለ፡፡ በኋላ የኖርዌይን ግዛት ደፈራችሁ ብንባልስ? (ኢንጂነሩ ለጦቢያ ክብር ሲሉ ቢታገሱ ጥሩ ነው!) በነገራችሁ ላይ የመኢአዱ የቀድሞ ሊ/መንበር ከኖርዌይ ኤምባሲ ጋር ሲወዛገቡ፣ የአንድነት ሊ/መንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ደግሞ ከአሜሪካ ኤምባሲ ጋር ተወዛግበዋል ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ (ተቃዋሚዎችንና ኤምባሲዎች የበላቸው ቡዳ አልታወቀም!) ኤምባሲው ለፓርቲው ሊ/መንበርና ለህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ቪዛ ተጠይቆ ለዶ/ር ነጋሶ እንጂ ለህዝብ ግንኙነት ሃላፊው አልሰጥም ማለቱ ነው ውዝግቡን ያስነሳው፡፡ (አሜሪካ ኤምባሲ መኪናና ቪላ ለሌለው ቪዛ አይሰጥም እኮ!)
እኔ የምላችሁ…በነገው ዕለት ሁለት ሰላማዊ ሰልፍ ያዘጋጁ ቡድኖች “እኔ ነኝ የቀደምኩት” በሚል ተፋጠዋል የሚባለው ከምር ነው እንዴ? እኔ እኮ ሰሞነኛ ቀልድ መስሎኝ ነበር፡፡
በጣም እኮ ነው የሚገርመው… (ለቀልድም እኮ አይመችም!) በአገር አመራር ደረጃ የምናስባቸው ወገኖች “እኔ ነኝ የቀደምኩት” የሚል ንትርክ እንዴት ይገጥማሉ? (የልጆች ፉክክር አስመሰሉት እኮ!) በሰላማዊ ሰልፎች የሚቀርቡ ጥያቄዎች በ24 ሰዓት ውስጥ ፈጣን ምላሽ ቢሰጣቸው እንኳ “እሺ ይሁን” ብለን እናልፈው ነበር፡፡
ግን ደግሞ እውነታው እንዲያ እንዳልሆነ አሳምረን እናውቃለን፡፡ በዚያ ላይ የጊዜ እጥረት እንደሌለብን እንኳን እኛ ነጮቹም ያውቁታል፡፡ (እዚህ አገር ርካሹ ነገር ምን ሆነና?) ታዲያ ለምኑ ነው እልህ መገባባቱ (ጐበዝ አገር በእልህ አትመራም!) እናላችሁ ሰልፉ ዛሬም …ነገም…ሳምንትም…የዛሬ ወርም ቢደረግ ችግሩ ምንድነው? (ወይስ አዋቂ ነግሮአቸው ነው!) በተለይ ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች…የሚያምርባችሁ እንደሰሞኑ የሃሳብ ፍልሚያ ስታደርጉ እንጂ እልህ ስትጋቡ አይደለም፡፡ (ከነገ በኋላ ሰላማዊ ሰልፍ ይታገዳል ተባለ እንዴ?)
እኔ የምለው… በፀረ ሽብር ህጉ ላይ ፓርቲዎች ባደረጉት ክርክር ማን የረታ ይመስላችኋል? አንዳንዶች “ተቃዋሚዎች አስገቡለት” ሲሉ ሰምቻለሁ - ለኢህአዴግ መሆኑ ነው፡፡ ለእኔ ግን ሁለቱም አሸናፊዎች ናቸው፡፡ ቁጭ ብለው መነጋገራቸው በራሱ ባለድል ያደርጋቸዋል፡፡ እኔ የምለው ግን አንድነት ጥይት የሆነ ወጣት ተናጋሪ ከየት አመጣ? ቀድሞ ኢህአዴግ የነበረና “ተገፍቶ” (ፖለቲካዊ በደል ደርሶበት ማለቴ ነው) የተቃዋሚውን ጐራ የተቀላቀለ ወጣት ነው የሚል አሉባልታ ሰምቻለሁ፡፡ እውነት ከሆነ ኢህአዴግ እንዴት እንደሚቃጠል አስቡት! (በራስ ጥይት መመታት እኮ ነው!) ምን ትዝ አለኝ መሰላችሁ… በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እየተገፉ ተሰደው ለሌላ አገር የሚሮጡ አትሌቶቻችን! በየውድድሩ እያሸነፉ የሌላ አገር ባንዲራ ሲያውለበልቡ አልተቆጨንም? (በእጅ ያለ ወርቅ እየሆነብን እኮ ነው!)
በመጨረሻ አንድ ሃሳብ ላቅርብና ልሰናበት (የሚሰማኝ ካለ) በሰሞኑ የፓርቲዎች ውይይት ኢህአዴግ “ፖለቲካዊ ውሳኔ” በሚል ባነሳው ጉዳይ ላይ ሌላ የውይይት ፕሮግራም ቢዘጋጅስ?
(ነገሮች እንዲጠሩ እኮ ነው!) አያችሁ ይሄ የውይይት ባህል ከዳበረ መፍትሔዎች ከውይይት መወለድ ይጀምራሉ፡፡ ኢቴቪም በዚያው አንድ ተወዳጅ ፕሮግራም ፈጠረ ማለት እኮ ነው፡፡ (ይሄም “ፖለቲካዊ ውሳኔ” ይፈልጋል እንዳትሉኝ?)

Saturday, 31 August 2013 12:05

መለስ የተዘከሩበት አሸንዳ

አሸንዳ እስከ 16ኛው መቶ ክ.ዘመን በመላ ኢትዮጵያ ይከበር ነበር
መቀሌ ስንደርስ የማለዳዋ ፀሐይ ከደመናው ጋር ግብግብ ገጥማለች፡፡ የመቀሌው አሉላ አባ ነጋ ዓለም አቀፍ አየር ማረፍያ ግን መደበኛ ተግባሩን እያከናወነ ነው፡፡ ከወትሮው በርከት ያሉ እንግዶቹን በማስተናገድ ተጠምዷል፡፡ እለቱ ደማቁ የአሸንዳ በአል የሚከበርበት ዋዜማ በመሆኑ የተስተናጋጁ ቁጥር የላቀ መሆኑን አቀባበል ያደረጉልን የትግራይ ባህልና ቱሪዝም ኤጀንሲ የስራ ባልደረቦች አረጋግጠውልናል፡፡ የአሸንዳ በአል የትግራይ ክልል ተወላጆች ከያሉበት ተሰባስበው መቀሌ የሚከትሙበት መሆኑንም ባጋጣሚው ለመታዘብ ችለናል፡፡ 

የበአሉን አከባበር እንድንታደም በቀረበልን ጥሪ መሠረት፣ በአዲስ አበባ ከሚገኙ የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት የተወከልን ጋዜጠኞች በኤጀንሲው የስራ ባልደረቦች አቀባበል ከተደረገልን በኋላ፣ ወደተዘጋጀልን ማረፊያ ነበር ያመራነው፡፡ በእርግጥም መቀሌ ውብና ጽዱ ነች፡፡ ሁላችንም ከጠበቅነው በላይ ሆና ስላገኘናት ተመሳሳይ አድናቆት ነበረ የቸርናት፡፡ ከምንም በላይ አስደናቂው የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች ቡና ወዳጅነት ነው፡፡ በእርግጥም “ቡና ጅማ ተመርቶ መቀሌ ይጠጣል መባሉ” ስህተት አይሆንም፡፡ ይህ የቡና ጠጪነት ባህል ለበርካታ ወጣቶችም የስራ እድል መፍጠሩን ለመታዘብ ችለናል፡፡
በክልሉ ባህልና ቱሪዝም ኤጀንሲ አስተባባሪነት የተዘጋጀው የበአሉ ዋዜማ “ካርኒቫል” ዋዜማውን አደመቁት አንዱ ነው፡፡ በዋዜማ ካርኒቫሉ ከትግራይ አምስት ዞኖች እና ከመቀሌ ከተማ ሰባት ክ/ከተሞች ተወክለው የመጡ የአሸንዳ ትርኢት አቅራቢዎች፣ በከተማዋ ዋና ዋና ጐዳናዎች በመዘዋወር ዋዜማውን ሲያደምቁት አምሽተዋል፡፡ ትርኢት አቅራቢ እንስቶቹ በባህል አልባሳት እጅግ ደምቀው ነበር፡፡ በልዩ ጥበብ ከተሰራው ሹሩባቸው ላይም የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ለማሰብ 4x4 የሆነ ነፍሳቸውን ይማርና የአቶ መለስን ፎቶ በክር አስረው ይታያሉ፡፡ አንዳንዶቹም በእጃቸው በተለያየ መጠን በተዘጋጁ የመስታወት ፍሬሞች የአቶ መለስን ፎቶ ይዘዋል፡፡ ለአሸንዳ በአል የሚዜመውን የባህሉን ግጥምና ዜማ ከተወጡት በኋላም መለስን የሚያሞግሱና የሚያወሱ ስንኞችን በዜማ አጅበው ያቀርቡ ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ እስከ በአሉ ፍፃሜ ባሉት ቀናት ሁሉ ተጥሏል፡፡ በነገራችን ላይ በ2004 ዓ.ም ከአቶ መለስ ህልፈት ጋር ተያይዞ አሸንዳ በክልሉ አልተከበረም ነበር፡፡ ዘንድሮም የሃዘኑ ድባብ በመጠኑ አለ፡፡ ለዚህም ይመስላል የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ኤጀንሲ በአሉን “ቃልህን ጠብቀናል ወደላቀ ደረጃም ለማሸጋገር ቃላችንን አድሰናል” በሚል መሪ ቃል ከአቶ መለስ የህልፈተ አመት መታሰቢያ ጋር ተያይዞ እንዲከበር የመረጠው፡፡ በዚህ መልኩ መቀሌና ጐዳናዎቹ በአሸንዳ ቆንጆዎች እንደተዋቡ ነበር ያመሹት፡፡
ነሐሴ 16 በሃይማኖቱና በባህሉ መሠረት ዋናው የአሸንዳ በአል የሚጀመርበት እለት ነው፡፡ የበአሉ ተሳታፊ ልጃገረዶች ማልደው በመነሳት ተሰባስበው አቅራቢያቸው ካለ ወንዝ እግራቸውን ታጥበው ቤተክርስቲያን ይሄዳሉ፡፡ በመቀሌ ያሉ ልጃገረዶችም ይህን ሲያደርጉ ተመልክተናል፡፡ ቤተክርስቲያን ተሳልመውም በበዓሉ ጭፈራ ካሰባሰቡት ገንዘብ ላይ የተወሰነውን አሊያም ሁሉንም ለታቦቱ ገቢ ሊያደርጉ ስለት ተስለውና ተማምለው ይመለሳሉ፡፡ ጭፈራቸውንም ከቤተክርስቲያኑ አቅራቢያ ካሉ ቤቶች ይጀምራሉ፡፡ በዚያው እንደየአካባቢው ሁኔታ ከ3-5 ቀን የሚቆየው የአሸንዳ ጨዋታ ይጀምራል ማለት ነው፡፡ በአንዳንድ የገጠር አካባቢዎች የአሸንዳ ጨዋታ እስከ መስቀል በአል እንደሚቀጥል ስለበአሉ ማብራሪያ የሰጡን ሊቀ ሊቃውንት ያሬድ ካሣ ነግረውናል፡፡
የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ኤጀንሲ አከባበሩን የበለጠ ለማስተዋወቅ ሲል በርካታ ህዝብ በተገኘበት በፌስቲቫልና ካርኒቫል መልክ ማክበር ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ በዘንድሮው በአልም ከየዞኑ ተወክለው የመጡ የአሸንዳ ትርኢት አቅራቢዎች፣ ከረፋዱ 3 ሰአት ጀምሮ ነበር በመቀሌ ስታድየም በመገኘት የየዞኖቻቸውን ባህላዊ ትርኢት ያቀረቡት፡፡ ከመቀሌ ከተማ እና ከየዞኖቹ ከመጡት ትርኢት አቅራቢዎች ባሻገርም ኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው የሚገኝ የከተማዋ እናቶችም የትርኢቱ ተሳታፊ ነበሩ፡፡
በስታድየሙ ከሚቀርበው ትርኢት ባሻገርም ህፃናት እና ልጃገረዶች በአሸንዳ ባህላዊ አልባሳት ተውበው የመቀሌን ከተማ ጐዳናዎች አስውበውና አድምቀው ነበር፡፡ በየቤቱ እየዞሩም የደንቡን ሲያደርሱ ውለዋል፡፡
በዚህ መልክ የመጀመሪያው ቀን ካለፈ በኋላም በቀጣዩ ቀን በመንገድ የሚያልፈውን ወንድ በመክበብ (ሓዛላይ ሓዛላይ አይትሰዓለይ) “ያዙልኝ ያዙልኝ እንዳትለቁት” እያሉ በመክበብ፣ በአሉን የሚያንፀባርቁ የሙገሳ ግጥሞችን በዜማ አዋህደው በማሞገስና በማወደስ ገንዘብ እንዲሸለሙ ያደርጋሉ፡፡ ገንዘብ የሰጣቸውንም “ፈሰሰ ከማይ ነሓሰ፤ በሃጐስ ገይሩ ብጥዓና ንዓመታ የጋንየነ” እንደ ነሐሴ ውሃ ፈሰሰ፣ ለመጪው አመት በሠላም በጤና ያድርሰን እያሉ ይመርቃሉ፡፡ አልሰጥም ያለው ደግሞ ስድብና እርግማን ይከተለዋል፡፡
በሶስተኛው ቀን ነሐሴ 18 የውድድር ቀን ነበር፡፡ ከየአካባቢው ተቧድነው እየዞሩ ሲጨፍሩ የነበሩ ልጃገረዶች፤ በየጐዳናው እየተሰባሰቡ በአጨፋፈርና በጭፈራ ድምቀት የሚወዳደሩበት እለት ነው፡፡ በእለቱም ከየዞኑ እና ከመቀሌ ከተማ የመጡ የትርኢቱ ተሳታፊዎች እርስ በእርስ ተወዳድረዋል፡፡ የፌስቲቫሉ አዘጋጆችም ለሁሉም ተወዳዳሪዎች ተመሳሳይ መጠን ያለው የቦንድ ሽልማት አበርክተውላቸዋል፡፡ አንዳንዶች በአሉ በፌስቲቫልና ካርኒቫል መልክ መካሄዷን የሚቃወሙት ቢሆንም ስለበአሉ ማብራሪያ የሰጡን ሊቀሊቃውንት ያሬድ ካሣ ግን ጉዳት የለውም ብለዋል - ባህል በየጊዜው እየጐለበተ እንደሚሄድ በመግለፅ፡፡

ጥቂት ስለ አሸንዳ
የበአሉን ባህላዊ አከባበር አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡን ሊቀሊቃውንት ያሬድ ካሣ፣ የአሸንዳ በአል በኢትዮጵያ መቼ እና እንዴት እንደተጀመረ ባይታወቅም በቀጥታ ከድንግል ማርያም ትንሣኤ ጋር ይያያዛል ይላሉ፡፡ የድንግል ማርያም ትንሣኤ ነሐሴ 16 ነው፡፡ ከዛን እለት ጀምሮ ደናግል ቅዱሳን እንስት ከመላእክቱ በተመለከቱት ስርአት መነሻነት ባህላዊ ነጫጭ ልብስ ለብሰው የወቅቱ መታሰቢያ የሆነውን ከለምለም የምድር ሳሮች ሁሉ ረዘም ያለውን “የአሸንዳ” ቅጠል በወገባቸው ዙሪያ አስረው ይጨፍራሉ፣ ያሸበሽባሉ፣ ይዘምራሉ፡፡ መነሻው ይሄ ሃይማኖታዊ ታሪክ እንደሆነ የሚናገሩት ሊቀሊቃውንት ያሬድ፣ በዚህ መልኩ እስከ 16ኛው መቶ ክ.ዘመን በመላ ኢትዮጵያ በአሉ በደመቀ መልኩ ይከበር ነበር ይላሉ፡፡ ባልታመቀ ምክንያት በዓሉ በሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ተረስቶ ዛሬ ላይ በትግራይ፣ በዋግህምራ እና በላስታ አካባቢ ብቻ ተወስኖ መቅረቱንም ሊቀሊቃውንት ጠቁመዋል፡፡ በአሁን ሰአት ደግሞ የትግራይ ክልል እንዲሁም የዋግህምራና የላስታ አስተዳደሮች ለበአሉ ትኩረት ሰጥተው የበለጠ እየዳበረ እንዲቀጥል ማድረጋቸው መልካም እንደሆነ ሊቀሊቃውንት ያሬድ ካሣ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡ በእርግጥም የአሸንዳ በአል በእነዚህ አካባቢዎች ተንከባካቢ ባለቤት አግኝቷል፡፡ የመስቀል በአልም በደቡብ ክልል በተለይ በጉራጌ ማህበረሰብ ዘንድ እንደ አንድ የብሔረሰቡ መገለጫ ተቆጥሮ በድምቀት ይከበራል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የጥምቀት በአል በጐንደር በፌስቲቫል መልክ በየአመቱ እየተከበረ ነው፡፡ ለብዙ ዘመናት ተረስቶ የነበረው የኢሬቻ በአልም በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ትኩረት ተሰጥቶት በባለቤትነት የሚከበር በአል ሆኗል፡፡ ነገር ግን ቀደም ሲል በተለይ በወንድ ታዳጊዎች ዘንድ ተወዳጅ የሆነውና ነሐሴ 13 ይከበር የነበረው የደብረታቦር (ቡሄ) በአል ግን ባለቤት አልባ ሆኖ እየጠፋ ያለ በአል ሆኗል፡፡ ሁሉንም ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ መሠረት ያላቸውን በአሎች ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ይቻል ዘንድ እነዚህን ለመሳሰሉ የተረሱ በአላትም ትኩረት መስጠት ይገባል፡፡

 

Published in ህብረተሰብ
Saturday, 31 August 2013 12:04

ሴቶች ለምን አይቀድሱም?

የወር አበባ የርኩሰት ምልክት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ቅዱስ ቁርዓን እንደሚነግሩን (ሳይንሱ የሚለውን እናቆየውና) የመጀመሪያው ሰው አዳም ነው፡፡ አዳም ብቻውን መኖር ስለማይችል፤ ስላልቻለም ሄዋን ተፈጠረችለት፤ ይኸ ማለት ወንድ ብቻውን ምሉዕ ሰው ሆኖ በተድላና ደስታ ህይወቱን መግፋት ስለማይችል የህይወቱ ሁነኛ አጋር ታስፈልገዋለች ማለት ነው፡፡ 

ፈጣሪ “ብዙ፤ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት” አለ እንጂ፤ አዳም ብቻውን ምድርን እንዲሞላት አልተፈቀደለትም፡፡ ለነገሩማ “ጽድቁ ቀርቶ በወጉ በኮነነኝ” እንደሚባለው ምድርን መሙላቱ ቀርቶ ራሱን ችሎ መኖር ስላቃተው ይመስለኛል ፈጣሪ ሴትን ለአዳም የፈጠረለት፡፡
የጽሑፌ ዓላማ ነገረ ሃይማኖት ላይ ያተኮረ ስለሆነ አንባቢያን እንዲገነዘቡልኝ የምሻውም በዚያው መሠረተ ሃሳብና ግልብጣዊ አተረጓጉሙን ነው። “ግልብጣዊ” ያልሁት የፈጣሪን ትዕዛዝ በአግባቡ አለመተግበር፤ ወይም ያላዘዘውን የእሱ ቃል አስመስሎ የመተርጐም አባዜ ያለ ስለሚመስለኝ ነው፡፡
ፈጣሪ “ብዙ! ተባዙ!”...ሲል “ተፈጥሮአዊ ግንኙነት ፈጽማችሁ ዘራችሁን አብዙ” ማለቱ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ለመውለድ፣ ለመባዛት ደግሞ ሁለት መሠረታዊ ጉዳዮች ያስፈልጋሉ፡፡
አንደኛው የሴቷ ቅድመ ማረጫ ጊዜ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በወንዱ በኩል ያለው አካላዊ ብቃትና ጤናማነት ናቸው፡፡ ከሁለቱ አንዱ ከጐደለ ዘርን ማብዛት አይቻልም፡፡
ነገር ግን ሙሴ እስራኤላውያኑን ከግብጽ ምድር መርቶ ሲና በረሃ ካደረሳቸው በኋላ የተለያዩ ሕግጋትን ማውጣት ጀመረ፡፡ ከሕግጋቱ መካከልም በወር አበባ ጊዜ ያለች ሴት ርኩስ መሆኗን፣ እሷ ብቻ ሳትሆን የተኛችበት አልጋ፣ የነካችው ዕቃ ሁሉ የረከሰ መሆኑን፣ እንዲሁም በወር አበባ ጊዜ ያለችውን ሴት የተገናኛት ወንድ ሁሉ ርኩስ መሆኑን የደነገገበት ሥርዓት ይጠቀሳል፡፡
ከእሱ በኋላ የተነሱ የሃይማኖት ተቋማትና መሪዎችም ይህንኑ መርህ እየቀባበሉ ተግባራዊ ሲያደርጉት ቆይተዋል፡፡ የዕምነት ተቋማት ብቻ ሳይሆኑ በባህላዊ ሥርዓት የሚመሩ አንዳንድ የዓለማችን ህዝቦች ዘንድም ሴት በምትወልድበትም ሆነ የወር አበባ ጊዜዋ ሲደርስ ከቤቷ እንደምትገለል አንዳንድ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡
ዛሬም ሴት ቤተክርስቲያን ቆማ ማስቀደስ ብትችልም መቀደስ ግን አይፈቀድላትም፡፡ ይህም ሐዋርያው ጳውሎስ “ሴት ትማር እንጂ በአደባባይ አታስተምር” ሲል ከሰጠው አስተምህሮ የተነሳ ይመስላል፡፡ ምክንያቱም የእነ ጳውሎስ መሠረት ኦሪት ነው፡፡ የወር አበባም “በሄዋን ስህተት ምክንያት የመጣ የመርገም ውጤት ነው” ብለው ያምናሉ፤ ይሰብካሉ፡፡
ዛሬም አንዳንድ ገዳማት ለሴቶች ጉብኝት እንኳ ፍጹም ክልክል ናቸው፡፡ ግን ለምን? ጥያቄዬ ከዚህ ነው የሚጀምረው፡፡ ሙሴ “በወር አበባ ላይ ያለች ሴት የረከሰች ናት…” ሲል ቃሉ ከፈጣሪ ሥልጣንና ጥበብ ጋር የሚጋጭ ይመስለኛል፡፡
ምክንያቱም፤ የወር አበባ ልክ እንደ ዛፉ፣ እንስሳቱ፣ ሰው፣ አራዊቱ ሁሉ የፈጣሪ ሥራ ነው። በመሠረቱ ዛፍ ካላበበ አያፈራም፡፡ እርግጥ ነው በሥራቸው የማያፈሩ ልዩ ተፈጥሮ ያላቸው ተክሎችና የሰብል ዓይነቶች አሉ፡፡ ሰውና እንስሳት ግን የዚያ ዓይነት ተፈጥሮ የላቸውም፡፡
ሴቶች ልክ እንደ ጽጌረዳ፣ ቡና፣ ማንጐ ወዘተ ዘር ሊሰጡ ካስፈለገ ማበብ አለባቸው፡፡ አበባቸው ቆመ ማለት ጠወለጉ ማለት ነው፡፡ ጠወለጉ ስል ከወር አበባቸው ፍጹም መቋረጥ በኋላ ዘር አይሰጡም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ሴቶች በወር አበባቸው ወቅት የረከሱ ከሆኑ ተስገብግበን የምንቀጥፋቸው፣ ወይም ለምንወደው የምናበረክታቸው አበባዎች ሁሉ ርኩሳን ናቸው ማለት ነው፡፡
በመሆኑም የወር አበባ የርኩሰት ምልክት ሊሆን አይችልም፡፡ በመሠረቱ ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደው ከሴት እንጂ ከወንድ አይደለም፡፡ የወር አበባ የምታየው ሴት የረከሰች ብትሆን ኖሮ ለምን ከ”ቅዱሱ” ወንድ አይወለድም ነበር? ወይም የመለኮቱን ተአምር ለማሳየት ሲል ከድንጋይ፣ ከዛፍ፣ ወይም ከእንስሳት ወዘተ ከአንዱ መወለድ የሚያቅተው አይመስለኝም። ሴት ከወንድ ይልቅ ቅድስትና ለመውለድ ከፈጣሪ የታደለች በመሆኗ ነው፡፡
አይሁድ አንዲት ጋለሞታ አምጥተው “ስትገለሙት” ወይም “ስታመነዝር ተገኝታለችና በድንጋይ ተወግራ ትሙት” ብለው ከኢየሱስ ፊት አቀረቧት፡፡ እሱ ግን “አዎ ትዕዛዜን ጥሳ ስታመነዝር ከተገኘች በድንጋይ ውገሯት” ከማለት ይልቅ “ከእናንተ ንፁህ የሆነው ይውገራት” አለና አሳፈራቸው፡፡ ከእሷ ጋር ነፍሳቸውን ሲያጡ እያደሩ ቀን “አመንዝራለች” ያሏት አይሁድም በሃፍረት ተሸማቀቁ፡፡
የኢየሱስን ትንሣኤ ቀድመው የተረዱትም ቅዱሳት አንስት እንጂ ሲከተሉት የኖሩት ሐዋርያት አይደሉም። ያ ቦታ ምንአልባት እኛ አገር ቢሆን ኖሮ “ሴቶች እንዲገቡ አይፈቀድም” መባሉ የሚቀር አይመስለኝም።
ዓለምን ያስጨነቁ ነገሥታትን፣ ደጋግ ጳጳሳትን፣ ቀሳውስትን፣ ምስኪን አርሶአደሮችን፤ ከሁሉም በላይ በፈጣሪም በሰውም ዘንድ ትልቅ ክብር ያገኙ ቅዱሳንን የወለደች ሴት እንጂ ወንድ አይደለም፡፡ ታዲያ የቅዱሳን እናት ለምንድን ነው ቤተ መቅደስ ገብታ የማትቀድሰው? አምጣ የወለደችው ቄስ፤ ለምን ከእሷ የተሻለ ክብር አግኝቶ በእሷ ላይ ሰለጠነ? መልሱ “ጉልበት ስላለው” የሚል ይመስለኛል፡፡
ያ ባይሆን ኖሮ ክርስቶስ ሰምራ ለዘመናት ስትጸልይባቸው በኖሩት ገዳማት ሴት እንዳትገባ አይከለከልም ነበር፡፡ ለነገሩማ እነሙሴ ዛሬ ቢኖሩ ኖሮ ያንን ህግ ሊያወጡ አይችሉም ነበር። ጳውሎስም የቅኔዋን ሊቅ ወ/ሮ ገላነሽ ሐዲስንና ሌሎችን ሊቃውንት ቢያይ ኖሮ “የሚሠሩትን አያውቁምና ይቅር…” ማለቱ አይቀርም ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡
ሌላው ቀርቶ ሴቶቹ ራሳቸው ተቀብለውት፣ ራሳቸውን እንደ በደለኛ አይተውት፣ ጉዳዩን “አዎ በበደላችን ምክንያት የመጣብን ስለሆነ ይቅር ይበለን” በሚል ስሜት ራሳቸውን ከቤተክርስቲያንም ሆነ ከጠበልና ከሌሎች ቦታዎች ሲያገልሉ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ ለነገሩ ጉዳዩ አያሌ ዘመናትን ያስቆጠረ ስለሆነ እንዲህ ማድረጋቸው ላያስደንቅ ይችላል፡፡
በበርካታ የኦርቶዶክስና የካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት ቅድስት ድንግል ማርያም፣ በእንግሊዝ ቅድስት ማርጋሬት፣ በሀገራችንም ማርያምን ጨምሮ ቅድስት ክርስቶስ ሰምራ፣ ቅድስት አርሴማ፣ እና በርካታ ሴት ጻድቃንና ሰማዕታት ቤተክርስቲያን በስማቸው ተሰርቶላቸው በወጉ ይከበራሉ፡፡
ክርስቶስ ሰምራን የመሳሰሉት እንዲያውም ትዳር መስርተው ልጅ የወለዱ ቅዱሳት ናቸው፡፡ እናም የወር አበባቸው አላረከሳቸውም፡፡ ለነገሩማ ዛሬ በአሜሪካ ለግብረ ሰዶማውያን ሳይቀር ግብረ ሰዶማዊ ጳጳስ ተሹሞ የካቶሊክን እምነት እየሰበከ ነው፡፡
ከዚህ የባሰ ርካሽ ነገር ምን አለ? ሆኖም ልብ ሊባል የምሻው ቁም ነገር፣ አሜሪካ ውስጥ ግብረሰዶማዊ ጳጳስ ስለተሾመ እኛም በዚህ አይነቱ የዘቀጠ ጉዳይ እንዘፈቅ ማለቴ አይደለም፡፡ ግን ሴቶች እና ያለባቸው ሰው ሰራሽ ጣጣ ሁልጊዜም ስለሚገርመኝ ነው ይህችን አጭር አስተያየት ለመጻፍ የተነሳሳሁት፤ እስኪ እንወያይበት?!

Published in ባህል
Page 2 of 17