“ሆራይዘን ቢዩቲፉል ፊልም ውዝግብ አስነሳ” በሚለው ዘገባ ”ብሉ ናይል የፊልም እና ቴሌቪዥን አካዳሚን የሚመለከት ዘገባ መውጣቱ ይታወሳል፡፡ ይሁን እና የቀረበው አጭር ዘገባ የተዛቡ መረጃዎችና ስህተቶችን የያዘ በመሆኑ እንደሚከተለው እንዲታረም እንጠይቃለን፡፡
ለመነሻ ያህል ሆራይዘን ቢዩቲፉል በብሉ ናይል የፊልም እና የቴሌቪዥን አካዳሚና ቴል ፊልም በተባለ የስዊዘርላንድ ድርጅት የተሰራ የትምህርታዊ ፕሮጀክት ፊልም ሲሆን፣ ትምህርት ቤቱ በፊልሙ ስራ የተሳተፈበት አላማም ተማሪዎቹ ልምድ ካላቸው የውጭ የፊልም ባለሞያዎች ጋር ጐን ለጐን የሚሰሩበትን ተግባራዊ ልምምድ በማመቻቸት፣ የፊልም ስራ ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ ማስቻል ነው፡፡
ተማሪዎች በትምህርታዊ ፕሮጀክቱ ላይ የሳተፉት ገንዘብ እንደሚከፈላቸው ተነግሯቸው ሳይሆን ከፕሮጀክቱ ለመማር እና ራሳቸውን የተሻለ የፊልም ባለሞያ ለማድረግ በሙሉ ፈቃደኝነትም ጭምር ነው፡፡ በፊልም ስራው ላይ ከተለያዩ የትምህርት ዘመን የተውጣጡ ከ35 በላይ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች የተሳተፉ ሲሆን፣ በፕሮዳክሽኑ መጨረሻ ከተማሪዎቻችን ጋር በተደረገው ግምገማ እና ውይይትም ትምህርታዊ ፕሮጀክቱ እጅግ ውጤታማ እና ተማሪዎቹ በርካታ ጠቃሚ እውቀት እና ልማዶችን ያካበቱበት መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
የጋዜጠኛዋ ዘገባ፣ በፊልሙ ላይ የተሳተፉ ተማሪዎች አካዳሚው የሚገባንን ክፍያ እንዲሁም አንድ አመት የተማርንበትን ሰርተፊኬት ከልክሎናል እንዳሉ ያትታል፡፡ “ሆራይዘን ቢዩቲፉል” ብሉ ናይል የፊልም እና ቴሌቪዥን አካዳሚ ቀደም ሲል ያስመረቃቸው እንዲሁም በወቅቱ በትምህርት ላይ የነበሩ ከ35 በላይ ተማሪዎች የተሳተፉበት ፊልም ነው፡፡ ጋዜጠኛዋ ክፍያ እና ሰርተፊኬት ተከልክለናል ያሉትን ግለሰቦች ስም ለመጥቀስ አልፈለችም፡፡ ከትምህርት ቤቱ ምክትል ስራ አስኪያጅ ጋር ባደረገችው ቃለ ምልልስ ሁሉንም ተማሪዎች እንደምታነጋግር ቃል የገባች ሲሆን ትምህርት ቤቱም በፊልሙ ላይ የተሳተፉትን ተማሪዎች ስም ዝርዝር እና ስልክ ቁጥር ሰጥቷት ነበር፡፡ ጋዜጠኛዋ በወቅቱ እንደገለፀችው “ከተማሪዎቹ አንዳቸውም እንኳን ከላይ ክፍያ እና ሰርተፊኬት ተከልክለናል በሚለው ባይስማሙ በዘገባው ላይ ይህ ጥያቄ የተማሪዎቹ ጥያቄ እንደሆነ አድርጐ ማውጣት አግባብ አይደለም” ብላለች፡፡ ይሁን እና ሁሉንም ተማሪዎች ይቅርና የተማሪዎቹን ድምጽ ለመወከል የሚበቃ ቁጥር ያላቸውን ሳታናግር ብሉ ናይል የፊልም እና የቴሌቪዥን አካዳሚ ከመላው ተማሪዎቹ ጋር ተቃርኖ ውስጥ የገባ በማስመሰል ለማቅረብ ሞክራለች፡፡ የጥቂት ግለሰቦች አጀንዳ የሆነን ጉዳይ ግለሰቦቹን በማንነታቸው ከማቅረብ ይልቅ “ተማሪዎች” ከሚል መከለያ ጀርባ በመደበቅ ለማራመድ መሞከር ተገቢ የጋዜጠኝነት ስነ ምግባር አይመስለንም፡፡
“ተማሪዎቹ ተከለከልን አሉ” ስለተባለው ሰርተፊኬት ጉዳይም ለጋዜጠኛዋ የሰጠነው መልስ “…ያላሟሉት ነገር ቢኖር ነው” የሚል የመላምት መልስ ሳይሆን የሚከተለውን ነው፡፡ በፊልሙ ላይ የተሳተፉት ከተለያየ አመት የተውጣጡ ተማሪዎች እንደመሆናቸው መጠን፣ ከፊሎቹ ትምህርታቸውን አጠናቀው ፊልሙ ከመጀመሩ በፊት ሰርተፊኬታቸውን የወሰዱ ሲሆን ቀሪዎቹ ደግሞ በወቅቱ በትምህርት ላይ የነበሩ ናቸው፡፡ ከእነዚህም መሀከል ከትምህርት ገበታ አለመቅረትን፣ የልምምድ እና የመመረቂያ ፕሮጀክት መስራትን እንዲሁም ስነ ምግባርን ጨምሮ በትምህርት ቤቱ መመሪያ መሰረት ማሟላት ያለባቸውን ቅድመ ሁኔታ ያሟሉ ተማሪዎች የመመረቂያ ሰርተፊኬት የወሰዱ ሲሆን ይህን ላላጠናቀቁ ተማሪዎች ሰርተፍኬት መስጠት ግን የትምህርት ቤቱ ደንብ አይፈቅድም፡፡
3. ዘገባው ብሉ ናይል የፊልም እና የቴሌቪዥን አካዳሚ ከቴል ፊልም ስዊዘርላንድ ጋር በመተባበር የሰራው ፊልም ወደፊት ትርፍ ከተገኘበት ለፀሐፊዎቹ 10% ይከፈላል እንዳለ ይገልጻል፡፡ ለጋዜጠኛዋ በሁለቱ ድርጅቶች መሀከል የተፈረመውን የፕሮዳክሽን ስምምነት ከነአማርኛ ትርጉሙ የሰጠናት ከመሆኑም በላይ በቃለ መጠየቁ ወቅት ቃል በቃል እያነበብን እንዳስረዳነው፣ ከፊልሙ ከሚገኝ ማናቸውም ገቢ የተጣራ ትርፍ ላይ ቴል ፊልም የተባለው የስዊዘርላንድ ድርጅት ለፊልሙ ዋና ፀሐፊ ለሆነው የውጭ ዜጋ 10 በመቶ የሚከፍል ሲሆን፤ ይህም በአራቱ ፀሐፊዎች መሀከል እኩል የሚከፋፈል ይሆናል፡፡ ብሉ ናይል ለፀሐፊዎች የ10 በመቶ ክፍያ ይከፍላል የሚል መረጃ አልሰጠንም፤ በፕሮዳክሽን ስምምነቱም ውስጥ የተገለፀው ይህን አይደግፍም፡፡
4. ዘገባው የፊልሙ ክፍያን በተመለከተ በተነሳው ውዝግብ ፊልሙ ለእይታ እንዳልበቃ ጠቅሷል፡፡ ይህ ዘገባ ስህተት ሲሆን ትምህርት ቤቱ እስከሚያውቀው ድረስ ፊልሙ ለእይታ ያልበቃው የፖስት ፕሮዳክሽን ስራው ተጠናቆ ባለማለቁ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ይህ ተጠናቆ ፊልሙ በተለያዩ የውጭ አገር ፌስቲቫሎች ላይ በመታየት ላይ መሆኑን ከፊልሙ የፌስ ቡክ ገጽ መረዳት ይቻላል፡፡ ፊልሙ በአገር ውስጥ ለመታየት ያልቻለውም እንደተባለው በክፍያ ውዝግብ ሳይሆን በፊልሙ ላይ ምንም መብት የሌለው እና የቀድሞ የትምህርት ቤቱ ተማሪ የነበረ ግለሰብ፣ ከትምህርት በቱ ፈቃድ ውጭ ፊልሙን ለማሳየት በዝግጅት ላይ መሆኑን ትምህርት ቤቱ በመረዳቱ እና ይህን ለማስቆም ለሚመለከታቸው አካላት ባቀረበው አቤቱታ መሰረት፤ ትምህርት ቤቱ የፊልም ባለቤትነቱን በማረጋገጥ ሂደት ላይ በመሆኑ ነው፡፡ ይህ ከተጠናቀቀ በኋላ ለእይታ የሚቀርብ ይሆናል፡፡ ከዚህ ውጭ ፊልሙ በሌሎች ወገኖች ለእይታ ቢቀርብ ግን ትምህርት ቤቱ ህጋዊ እርምጃ የሚወስድ ይሆናል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ጋዜጠኛዋ ያቀረበችው መረጃ የአንድ ወገን እይታን ብቻ ያንፀባረቀ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡
ዘገባው ተማሪዎቹን እና ጸሀፊዎቹን ለያይቶ ለማቅረብ ያልቻለ ቢሆንም የፊልሙ ጸሀፊዎች የፊልሙን ጽሁፍ በሚያዘጋጁበት ጊዜ እያንዳንዳቸዉ 2500 ብር ብቻ እንደተከፈላቸዉ እና ለትራንስፖርት እና ሌሎች ወጪዎች ከኪሳቸዉ ሲያወጡ እንደነበረ ይገልጻል፡፡ አሁንም የጸሀፈዎቹን ስም ለመግለጸ እንዳልተፈለገ ልብ ይሏል፡፡ በቃለ መጠይቁ ወቅት ጋዜጠኛዋ ጸሀፊዎቹ ምንም አይነት ክፍያ እልተሰጠንም እንዳሏት ገልጻ፣ ይህ ለምን እንደሆነ ጠይቃለች፡፡ በምላሹም ይህ ስህተት እንደሆነ እና ምንም እንኳን ፊልሙ ትምህርታዊ ፕሮጀክት ቢሆንም ጸሀፊዎቹ በስራ ወቅት ለሚያወጡት ወጪ እና ከሌላ ስራ ያገኙት የነበረዉን ገቢ በጥቂቱም ቢሆን ለማካካስ በየወሩ 2500 ብር ሲከፈላቸዉ እንደነበረ፣ ለትራንስፖርት እና ሌሎች ወጪዎችም ባቀረቡት ደረሰኝ መሰረት እንደተከፈላቸዉ ገልጻ ለዚህም በእጃችን የነበረዉን ማስረጃ አሳይተናል፡፡ ይሁን እና ጋዜጠኛዋ የእኛን መልስ እና ማስረጃ ወደጎን በመተዉ ይልቁንም ያቀረብነዉን ማስረጃ እነዚህ ግለሰቦች የሰጡትን የተሳሳተ ማስረጃ “የተከፈለን 2500 ብር ብቻ ነዉ” ወደሚል ማስተካከያ ለመቀየር ተጠቅማበታለች፡፡ አንድ ጋዜጠኛ የተሰጠዉ መረጃ ስህተት አንደነበረ የሚያረጋግጥ መረጃ ሲደርሰዉ ይህን እንዳላዩ ማለፍ እና ይበልጡንም የሀሰት ማስረጃ የሰጡትን ግሰቦች ቃል ለማስተካከል መጠቀሙ ወገንተኝነትን የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ የጋዜጠኛዉን ሀቀኝነት እና ተአማኒነት ጥያቄ ዉስጥ የሚጥል ነዉ፡፡
በዘገባዉ የቀረበዉ የገንዘብ መጠንም እንዲሁ ገንዘቡ ወደብር ሲለወጥ በፊልሙ ዝግጅት ወቅት ከአንድ አመት ከሰባት ወር በፊት ባለው የምንዛሪ ሂሳብ ሳይሆን ዛሬ ባለዉ በመሆኑ ስህተት ነዉ፡፡ በዚህም መሰረት የገንዘብ መጠኑ እንደተባለዉ 360,400 ብር ሳይሆን 252,000 ብር ነው፡፡
ከላይ የተገለጻዉን ገንዘብ አጠቃቀም በተመለከተም ብሉ ናይል የፊልም እና ቴሌቪዥን አካዳሚ ከተቋቋመበት አላማም ሆነ “ከሆራይዘን ቢዩቲፉል” ትምህርታዊ የፊልም ፕሮጀክት አላማ አኳያ፤ ትምህርት ቤቱ ገንዘቡን በደሞዝ መልክ ማከፋፈል ሳይሆን ተጨማሪ ትምህርታዊ የፊልም ፕሮጀክቶችን በመስራት ነባር እና መጪ ተማሪዎች ክህሎታቸዉን እንዲያዳብሩ የማድረግ አቋም ያለዉ መሆኑን እንገልጻለን፡፡
ከሰላምታ ጋር
ብሉ ናይል የፊልም እና የቴሌቪዥን አካዳሚ

Published in ዜና

ለስልጠና ወደ ደቡብ ኮርያ ተልከው እዚያው ጥገኝነት ጠይቀው የቀሩት 39 ኢትዮጵያውያን፤ የኢትዮጵያን መንግሥት በመቃወም የፊታችን ረቡዕ በደቡብ ኮርያ ዋና ከተማ ሴኡል የተቃውሞ ሰልፍ እንደሚያደርጉ አስታወቁ፡፡
በአውቶ መካኒክ፣ በዌልዲንግና በኤሌክትሪሲቲ ሰልጥነው ተመልሰው ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ መንግሥት የላካቸው እነዚህ ወጣቶች፤ በችግር ላይ እንደሆኑ ተደርጐ የተነገረው ሐሰት መሆኑን ጠቅሰው፤ ሰብአዊ ክብራቸውና መብታቸው ተጠብቆላቸው በሴኡል እየኖሩ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ወጣቶቹ የፊታችን ረቡዕ “በኢትዮጵያ ያለው የሰብአዊ መብት ጥሰት ይቁም”፣ “የሙስሊም ወንድሞቻችን ችግር እኛንም ይመለከተናል”፣ “መንግሥት ከሃይማኖት ጉዳዮች ላይ እጁን ያንሳ” የሚሉ ጉዳዮችን በማንሳት በሴኡል ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚያካሂዱ ከስፍራው በስልክ ገልፀዋል፡፡

Published in ዜና

ከአዘጋጁ፡- የድምፃዊ ኢዮብ መኮንን ድንገተኛ ህልፈትን ተከትሎ በፌስቡክ ላይ ከወጡ በርካታ አስተያየቶች ጥቂቶቹን እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡ ለባለቤቱ፣ ለቤተሰቡና ለወዳጅ ዘመዶቹ መፅናናትን እንመኛለን፡፡
ከጥቂት አመታት በፊት አንድ የበጎ አድራጎት ትርኢት ላይ ለመሳተፍ፣ ከዘፋኞች ጋር ወደ ደሴ ተጉዤ ነበር፡፡ የተሣፈርንበት አውቶብስ ጉንጫቸውን በጫት አሎሎ በወጠሩ ዘፋኞች ተሞልቷል፡፡ ዘፋኞቹ ሲሻቸው ይተራረባሉ፣ሲሻቸው ይጮሃሉ፣ይጨፍራሉ፡፡ የአውቶብሳችን ሽማግሌ ሹፌር ሳይቀር፣አልፎ አልፎ መሪውን እየለቀቀ በማጨብጨብ፣ በ ‹‹ቅወጣ›› ከዘፋኞች እንዳማያንስ በማሳየት ላይ ነበር፡፡ በጫቱም፣በጭፈራውም የሌለበት ድምጻዊ ኢዮብ መኮንን ብቻ እንደሆነ ተመለከትሁ፡፡ በእርጋታ ተቀምጦ፣ በአውቶብሱ መስኮት አሻግሮ የሚሮጡ የግራር ዛፎችን ይመለከታል፡፡ ልዩነቱ ግልጽ ነበር፡፡
ድሮ ድሮ፣ ኢዮብ መኮንን አቤሴሎም የሚዘናፈል ረጅም ጸጉር ያለው ጎልማሳ ነበር፡፡ ድንገት ጸጉሩን ተሸለተ፣ ከጸጉሩ ጋር የጥንት ባህርይውን አራገፈ። ጭምት፣ መንፈሳዊና በመጽሐፍ ቅዱስ ፍቅር የነደደም ምዕመን ሆነ፡፡
በተገናኘን ቁጥር፣ኢዮብ ስለእምነት እንድንወያይ ይፈልጋል፡፡ ብዙ ጊዜ እምነት የሚያጠብቅ ሰው አንዳች ችግር ይኖርበታል ብዬ አስብ ነበር፡፡ ኢዮብ ግን እጅግ መልካም ሊባል በሚችል ሕይወቱ፣ ይሄንን አመለካከቴን ውድቅ አድርጎብኛል፡፡
የዛሬ ሳምንት ገደማ ኢዮብ ዘፈን በመሥራት ላይ ነበር፡፡ እና ለአንድ ዜማው ግጥም እንድሠራለት ጋበዘኝ፡፡ ከዚህ በፊት የሞከርኳቸው የዘፈን ግጥሞች ስለከሸፉብኝ ግብዣውን ለመቀበል አመነታሁ፡፡ ግን ደሞ ወዲያው፣በኢዮብ ድምጽ ግጥሜ ተዘፍኖልኝ ለማየት ጓጓሁ፡፡ ውሀ ልማት አካባቢ፣ሌክስ ፕላዛ ሕንጻ ሥር መኪናው ውስጥ ቁጭ ብለን ዜማዎችን ማድመጥ ጀመርን፡፡ ዘፈኑ ውስጥ ያሉት ሐሳቦች አብዛኞቹ ወደ መዝሙር ያዘነብላሉ፡፡ ኢዮብ ዘፈኑን ለፈንጠዝያ ሳይሆን ለስነምግባር ግንባታ ሊጠቀምበት ፈልጓል፡፡ አንድ በጣም ልብ የሚበላ የሶማሌ ዘፈን አስደመጠኝ፡፡
‹‹ሶማሊኛ ትችላለህ እንዴ?>>
‹‹አዎ፣ትግርኛም አውቃለሁ!››
‹‹የት ተማርከው?>>
‹‹አስመራ፣ የወታደር ልጅ መሆኔን አትርሳ››
ከዘፈን ውጭ ምን ታደርጋለህ?
‹‹ኦን ላይን፣ጊታር እየተማርሁ ነው፡፡ ቆይ ላሳይህ››…ላፕቶፑን ለኮሰና ጥቂት አስጎበኘኝ፡፡ ከዛ ከመኪናው ስወርድ የመኪናው እጀታ ስለማይሠራ ወርዶ ከውጭ ከፈተልኝ፡፡ ኢዮብ ብዙ ብሮችን መቁጠር የሚችል ልጅ እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ እንኳን መኪናውን የመኪናውን እጀታ ማስቀየር አልፈለገም፡፡ ምናልባት፣ዓመት በአልን ጠብቆ ልብስ የሚቀይር ብዙ ሰው ባለበት አገር ውስጥ፣መኪና መቀያየሩን እንደ ኃጢአት ቆጥሮት ይሆናል፡፡
ከጥቂት ቀናት በኋላ ልኡል የተባለ ዘፋኝ ጓደኛዬ፣ የኢዮብን በድንገት መውደቅ ሲነግረኝ ወደ ቅዱስ ገብርኤል ሆስፒታል ሄድኩ፡፡ ዘፋኞችና አዘጋጆች መጠበቂያው ክፍል ላይ ተደርድረው ይተክዛሉ፡፡ ዘሪቱ፣ ዳግማዊ አሊ፣ እቁባይ በርሄ፣ አጃቸውን አገጫቸው ላይ ጭነው፣ ተቀምጠዋል። የኢዮብ ባለቤት ወዲያ ወዲህ እየተንቆራጠጠች ታነባለች፡፡
ዛሬ ደግሞ ይሄው ሞቱን ሰማሁ፡፡ኢዮብ!!! በጠፈሩ ውስጥ፣ ያለግብ ከሚዞሩ ኮረቶች፣ ያለ ምክንያት ከሚበሩ ኮከቦች በቀር ምንም የለም ብዬ እንደማምን ታውቃለህ፡፡ ይሁን እንጂ ለዛሬ እንኳ፣ የኔ እምነት ከሽፎ ያንተ እምነት እውነት እንዲሆን እመኛለሁ፡፡ በምድር ለገጠመህ መራራ እጣ ሰማያዊ ካሳ (ጉማ) እንድታገኝ እመኛለሁ፡፡
(በዕውቀቱ ስዩም ከፌስ ቡክ)
ኢዮብ የስራ ባልደረባዬ ብቻ ሳይሆን የቅርብ ጓደኛዬም ነበር፡፡ ለሶስት ተከታታይ ዓመታት በፋራናይት ክለብ አብረን ሰርተናል፡፡ ይሄ ቅርብ ግንኙነት እንዲኖረን አድርጐናል፡፡
እኔና ኢዮብ የወንድማማቾች ያህል ነበር። የአስር ዓመት ጓደኝነት ከዚያ ውጭ ምን ሊሆን ይችላል? የኢዮብ ሞት ለእኔ ያልጠበቅሁትና በጣም አስደንጋጭ ነበር፡፡ ወደ ኬንያ ለህክምና ሲሄድ ተሽሎት ወደ አገሩ እንደሚመለስ ጽኑ እምነት ነበረኝ፡፡ ኢዮብ ከእንግዲህ አብሮን እንደማይኖር የሰማሁትን ዜና አሁንም ድረስ አምኖ መቀበል አዳግቶኛል፡፡ ኢዮብ የሚገርም ተሰጥኦ የታደለ ታላቅ አርቲስት ነበር፡፡ ይሄን ተሰጥኦውን ገና በቅጡ ሳይጠቀምበት ህይወቱ አለፈ፡፡ ብዙ አስደናቂ ችሎታዎቹን ለማየት በምንጠብቅበት ሰዓት ነው ሞት የቀደመው፡፡ አሁን ምን ማለት አይቻልም - እግዚአብሔር ነፍሱን በሰላም እንዲያሳርፍለት ከመፀለይ በቀር፡፡
(ድምፃዊ ሸዋንዳኝ ኃይሉ)
ይሄንን ባለተሰጥኦ ድምፃዊ ለማወቅና ለመተዋወቅ የቻልኩት አንድ ግሩም ወዳጄ ሥራውን በዳላስ፣ ቴክሳስ ሲያስተዋውቅለትና በመስከረም ወር 1997 ዓ.ም ለኮንሰርት ባመጣው ጊዜ ነበር፡፡ ኢዮብ ያኔ “እንደ ቃል” የተሰኘው አዲሱ አልበሙ ወጥቶ ስለነበር ዝናው መናኘት ጀምሯል፡፡ “ኢትዮ - ሬጌ” የተባለ አዲስ የሙዚቃ ዘይቤ ለኢትዮጵያ በተለይ ለዳያስፖራው ያስተዋወቀ አዲስ ዘፋኝ በሚል ነበር የሚታወቀው፡፡ ከዜማው የበለጠ የዘፈን ግጥሞቹ ማራኪ ነበሩ፡፡ ፍቅርን፣ መከባበርንና ትሁትነትን በዘፈኖቹ ሰብኳል፡፡ ኢዮብን በሞት ብናጣውም ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ባበረከተው ታላቅ አስተዋጽኦና በትሁት ባህርይው ዘላለም ሲታወስ ይኖራል፡፡
ዳኒ (ከዋሺንግተን ዲሲ)
ከሁለት ዓመት በፊት ኢዮብ በኒውዮርክ ያቀረበውን ኮንሰርት የመታደም ዕድል አግኝቼ ነበር። ገና በመጀመሪያውና ብቸኛ በሆነ አልበሙ ዝነኛ ለመሆን የበቃ አርቲስት ነው፡፡ ያለጊዜው ህይወቱ ማለፉ በጣም ያሳዝናል፡፡
ቢኒያም ጌታቸው (ከአሜሪካ)
የቅርብ ጓደኛው አልነበርኩም፡፡ እኔን ጨምሮ በአብዛኛው ሰው ዘንድ ይወደድ እንደነበር ግን አውቃለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ተወዳጅ የነበረ ወጣት የሬጌ አቀንቃኝ አጥታለች፡፡ እግዚአብሔር ነፍሱን በመንግስተ ሰማያት ያኑርለት፡፡ ለቤተሰቡ መጽናናትን እመኛለሁ፡፡
ለማ ገብረማርያም (ከኢትዮጵያ)
ልብን የሚያላውስ ዘፋኝ ነበር፡፡ አዲስ አበባ እያለሁ ኮንሰርቶቹንና በምሽት ክለብ የሚያቀርባቸውን ሥራዎች ታድሜያለሁ፡፡ በተለይ በክለብ H20 እና በፋራናይት በሚያስገርም ድምፁ መድረኩን የቀወጠባቸውን ሌሊቶች ፈጽሞ አልረሳቸውም፡፡ የእሱ ሞት በተለይ ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ትልቅ እጦት ነው፡፡ ሁላችንም አዲሱን አልበሙን እንጂ ሞቱን አልጠበቅንም ነበር፡፡ በጣም አስደንጋጭ ዜና ነው፡፡
አለማየሁ ጨቡዴ (ከኩዌት)
በአዲስ አበባ ኮንሰርቶቹን ተከታትያለሁ፡፡ በምሽት ክበቦች ሲዘፍን ታድሜያለሁ፡፡ ዘፈኖቹን በመኪና ውስጥ፣ እቤቴና ቢሮዬ እሰማቸዋለሁ። በዘፈኖቹ ተለክፌ ነበር ማለት እችላለሁ፡፡ ጂም አብረን ስንሰራ ከስፖርት በኋላ ስቲም ውስጥ እናወራለን፡፡ በጣም አሪፍ ሰው ነበር - ለጨዋታና ለጓደኝነት የሚመች፡፡ ሁላችንም ነን ያጣነው፡፡ የእሱ ሞት ለሁላችንም ትልቅ ጉዳት ነው፡፡
ብሩክ ኢትዮ (አዲስ አበባ)
አሁንም ድረስ ከድንጋጤ አልወጣሁም፡፡ እኔና ኢዮብ የፌስቡክ ጓደኛ የሆንነው ሙዚቃውን ከሰማሁ በኋላ ነው፡፡ የዓለም ተጓዦች የሆኑ ሰዎች ሲዲውን ይዘውት ስለነበር ከእነሱ ተውሼ ነው ያደመጥኩት፡፡
በቅርቡ ካሊፎርኒያ ለኮንሰርት በመጣ ጊዜ “All night pressure” የተባለው የእኔ ባንድ እንዲያጅበው ተስማምተን ነበር፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ አልተሳካም፡፡ የሁለተኛ አልበም ቀረፃችንን ለመጨረስ ውጥረት ውስጥ ነበርን፡፡
ከኢዮብ ጋር ባወራንባቸው ጥቂት ጊዜያት ሃቀኛ ነፍስ እንደነበረውና ሲበዛ ደግ መሆኑን ለመገመት አልቸገረኝም፡፡ የግጥሞቹ ትርጉም ባይገባኝም ድምፁና አዘፋፈኑ ውብና አይረሴ ነበር፡፡ ሙዚቃ ክልልና ድንበር ተሻጋሪ ለመሆኑ ይሄም ተጨማሪ አብነት ነው፡፡ በዚህ ሰዓት በጣም አዝኛለሁ፡፡ ለባለቤቱና ቤተሰቦቹ መልካሙን ሁሉ እመኛለሁ። በዚህ የሀዘን ጊዜ በፀሎት ከጐናችሁ መሆኔን ለመግለፅ እፈልጋለሁ፡፡
ክሪስ ኤሊስ (ኦሬንጅ ካንቲ፣ ዩኤስኤ)

==============
ድምጻዊ እዮብ መኮንን ዘውዴ ከአባቱ ከአቶ መኮንን ዘውዴ ይመኑ እና ከእናቱ ወ/ሮ አማረች ተፈራ የምሩ ጥቅምት 12 ቀን 1967 ዓ.ም በጭናቅሰን ገብርኤል ጅጅጋ ከተማ ተወለደ፡፡ እድሜው ለትምህርት ሲደርስ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በጅጅጋ አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፤ከፊል የሁለተኛ ደርጃ ትምህርቱን ደግሞ ከወላጅ አባቱ ጋር ወደ አስመራ በመሄድ የተከታተለ ሲሆን፤ቀሪውን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ ወደ ጅጅጋ በመመለስ ተምሯል፡፡ በ1991 ዓ.ም. በአጋጣሚ ወደ አዲስ አበባ የሚያመጡ ፈቃደኛ ሰዎች በማግኘቱ እራሱን ያስተዳድርበት የነበረውን የፎቶግራፍ አንሺነት ሥራን ትቶ፣ በ24 ዓመቱ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ካዛንቺስ አካባቢ በሚገኘው የያኔው ፋልከን ክለብ ድምጻዊነቱን “ሀ” ብሎ ጀመረ።
ከ1991 ዓ.ም. ጀምሮ አልበሙን እስካወጣበት 2000 ዓ.ም ድረስ የሌሎች ድምጻውያንን ሥራዎች፣በዋነኝነት የአሊ ቢራን እና የቦብማርሊን ዘፈኖችን ሲያቀነቅን የቆየ ሲሆን በነዚህ ጊዜያት ከኢትዮጵያ ውጭ ወደ ዱባይም በመመላለስ በድምጻዊነቱ ሰርቷል፡፡ በጥቅምት 2000 ዓ.ም በአብዛኛው በሬጌ ስልት የተዘጋጀው “እንደቃል” የተሰኘው የመጀመሪያ አልበሙ ከተለቀቀ አጭር ጊዜ በኋላ፣ በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነትን በማትረፍ እስካሁን ድረስ በከፍተኛ መጠን በመደመጥ ላይ ይገኛል፡፡ በአዲስ ጣዕም የመጣው “እንደቃል” አልበም በኢትዮጵያ ውስጥ የሬጌ ሙዚቃ ይበልጥ ይወደድ ዘንድ ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጥሯል።
ከዚህ አልበሙ በኋላ በሀገር ውስጥ እና ከሃገር ውጪ በአውሮፓ እና በአሜሪካ የሙዚቃ ዝግጅቶችን እያቀረበ ቆይቷል፡፡ በአዲስ አበባ የተለያዩ የሙዚቃ ቦታዎች ላይም ለረጅም ጊዜያት በቋሚነት የራሱን ዘፈኖች ለአድናቂዎቹ በመድረክ ሲያቀርብ ነበር፡፡ ሁለተኛ አልበሙንም በመሥራት ላይ የነበረ ሲሆን በድንገት እስኪታመም ድረስ ሙሉ ትኩረቱ በዚሁ ሥራው ላይ ነበር፡፡ ድምጻዊ እዮብ መኮንን ነሐሴ 7 ቀን 2005 ዓ.ም በድንገተኛ የስትሮክ ህመም መኖሪያ ቤቱ ደጃፍ ላይ የወደቀ ሲሆን፤ህመሙ ጠንቶ እራሱን ሳያውቅ በቅዱስ ገብርኤል ሆስፒታል የህክምና ክትትል ሲደረግለት ቆይቶ በወዳጅ ዘመዶቹ ርብርብ ለተጨማሪ ህክምና ወደ ናይሮቢ ኬንያ ሄዶ፣ በአጋካን ሆስፒታል ሕይወቱን ለማትረፍ ጥረት ቢደረግም በታመመ በአምስተኛ ቀኑ ነሐሴ 12 ቀን 2005 ዓ.ም. ምሽት በ38 ዓመቱ ሕይወቱ አልፏል፡፡
ድምጻዊ እዮብ መኮንን ባለትዳር እና የአንድ ልጅ አባት ነበር። የድምጻዊ እዮብ መኮንን የቀብር ስነ-ስርዓት ባለፈው ረቡዕ ነሐሴ 15 ቀን 2005 ዓ.ም ቤተሰቦቹ፣ወዳጅ ዘመዶቹ እና አድናቂዎቹ በተገኙበት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል።

Published in ጥበብ

… በጫጫታው መሀል ዝም ማለት … አድማጭ ያደርጋል፡፡ የሚደመጥ ነገር ሳይኖር ዝም የሚል ግን በህይወት አለመኖሩን እንዳረጋገጠልን ይቆጠራል። ህይወት እንዳልሞተች የምናረጋግጠው ህያው ነኝ ባይ ሲገልፃት ነው፡፡ የሞተው ሰውዬ ስብሐት ገ/እግዚአብሔር መሆኑኑ ተማምነን ቀብረነው ነበር። አሁንም ግን መግለፁን ቀጥሏል፡፡ … አልሞተም ማለት ነው፡፡ ወይ እኛ ሞተናል፡፡
ስብሐት ሞቶም እያነጋገረን ነው፡፡ አንዳንድ ሙታንን ልንቀብራቸው አንችልም፡፡ አንደፍርም። ሞተው ቢመሩን እንመርጣለን፡፡ በህይወት ያለነው ከእነሱ ጋር አንመጥንማ! እነሱን በማሞገስ አልያም እነሱን በመርገም ብቻ ነው አለመሞታችንን የምናረጋግጠው፡፡ እረፍት ልንሰጣቸው አንችልም። እነሱን ሳንመረኮዝ ምን ላይ እንቆማለን? ከእነሱ መቃብር ጋር የእኛ ትንሳኤ ተሳስሯል፡፡ የኛ የትንንሾቹ ሰዎች፡፡ We stand on the shoulder of giants not to see further … በህይወት መኖራችን ራሱ ስለሚያጠራጥረን ነው፡፡
በጫጫታው መሀል ዝም ማለት አልቻልኩም። … ሚልኪ ባሻ ጀመረው፡፡ ሙታንን ቀስቅሶ ማናገሩን፡፡ ጠርጢዎስ መለሰለት፡፡ ጠርጢዎስ ከቫቲካን … ሁሌ መልስ ነው የሚሰጠው፡፡ መልሱ ላልተጠየቀበት ጥያቄ መሆኑ የለመድነው አባዜው ነው፡፡ … የሆነ ነገርን ሁሌ መመርኮዝ ያስፈልገዋል። “መንጠልጠል” ያለው የአለፈው ሳምንት ፀሀፊ ጠርጢዎስን በተለይ ይገልፀዋል፡፡ … ጠርጢዎስ፡- reacts on Issues before acting towards them … ከዚህ በፊት በሀይማኖት ክርክሮች ላይ አይተነዋል፡፡ በሰው ሀሳብ ላይ ከመመርኮዝ አልፎ … መገንደስ ይወዳል፡፡ “ጥሪዬ ነው” ብሎ ወደሚያምንበት ሀይማኖቱ አቅጣጫ ነው የሚገነደሰው፡፡ ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡ እንደዛ አይነት ሰው ነው … It takes all kinds!
መጀመሪያ ሰላሳ ሰዎች ሆነን በሰውየው ትከሻ ላይ ወጣን፡፡ ሩቅ ለማየት ወይንም ስብሐትን ለመግለፅ ሳይሆን … ራሳችንን ለመግለፅ ወይንም ለማየት ብለን ነው፡፡ ሰውየው ሞቷል፡፡ እኛ ስናመሰግነውም ሆነ ስንሰድበው አይሰማውም። ስለዚህ፤ ምስጋናውም ሆነ ክብሩ … ጥቅሙም ሆነ ጉዳቱ … ለተንጠለጠልንበት ሀውልት ሳይሆን ለእኛው ነው፡፡
እሺ! … ሰላሳ ሰዎች የተንጠለጠሉበት መፅሐፍ በሰላሳ ሺ ሰዎች (ወይንም በላይ) እየተነበበ ሊሆን ይችላል አሁን፡፡ በሰላሳ ሺ አፎች ስለ መፅሐፉ ይወራል፡፡ የተወራው በሀምሳ እጥፍ ተባዝቶ ይራገባል፡፡ ይሄ ሁሉ ሰው ስለ ስብሐት ሲያወራ፤ የስብሐት መልክ እንደ አነበበው ተመልካች እይታ ብዙ ሆኖ ቢሆን “እሰየው” ነበር፡፡ “ስብሐት የሰውን ሁሉ መልክ ይመስላል፤ ወይንም ስብሐት ህይወትን በሙሉ የሚመስል ገፅታ አለው … ስብሐት ህይወት ነው፤” ብለን እንስማማ ነበር፡፡ አሁን ባልኩት ብዙ ገፅታ መስማማት ማለት፤ ህይው መሆን ማለት ነው፡፡ እኛም ሆነ ስብሐት በእኛ ውስጥ ወይንም አማካኝነት ህያው ሆነ ማለት ነበር፡፡
ለምሳሌ፤ የአጋፋሪ እንደሻሁ (ገፀ ባህሪ) በእርግጠኝነት የጥበብ (ውበት) ልኬት ናቸው፤ ካልን… የህይወትም ልክ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ጥበብ ህይወትን አጠቃሎ የሚወክል፣ የሚገልፅ፣ የሚተረጉም ነገር ስለሆነ ነው፡፡ በአጋፋሪ እንደሻው አማካኝነት ራሳችንን ማየት ካቃተን፣ ድርሰቱ ለህይወት፣ ከህይወት … ለህያዋን አይደለም፡፡ በአጋፋሪ እንደሻው ራሳችንን ማየት ቢያቅተን እንኳን … ቢያንስ ስብሐትን እንዳናይ መጠንቀቅ ነበረብን፡፡
“ሀምሌትን ስናይ ሼክስፒርን አየን” ከማለት አይተናነስም፡፡ ያሳዝናል … ያሳፍራል፡፡ ስብሐት ምን ያድርግ … ሌቱም አይነጋልኝ ላይ ስላለው የክንፈ ገፀ ባህሪ? የሌቱም አይነጋልኝ መፅሐፍን በዛሬው እለት ከገበያ ገዝቶ ቤቱ ገብቶ እሚያነብ ሰው ተጠያቂ የሚያደርገው ለንባቡ (አንብቦም ለመፀየፉ) … ያው የፈረደበትን ስብሐት ነው፡፡ ሰውየው እኮ ሞቷል፡፡ … ለኒዩክሊየር ጦር መሳሪያ ስጋት ኤንሪኮ ፈርሚ እና አንስታይን ምን ያድርጉ? … ጦር መሳሪያውን አሁን ያለ ሰው ነው ለክፉም ሆነ ደግ መርጦ የሚጠቀምበት … የቦንቡ መነሻና መድረሻ አሁን ያለ ሰው ራሱ ነው።
በ “ሌቱም አይነጋልኝም” ውስጥ ያለው ገፀ-ባህሪ ሳይሆን አሁን በማንበብ ላይ ያለ ሰው ነው ልክ ወይንም ስህተት፡፡ በሀምሌት ገፀ ባህሪ ውስጥ ሼክስፒርን ይቅርና … ሀምሌትንም ራሱን በማይቀያየር መልክ አናገኘውም፡፡ የኢትዮጵያዊው ሀምሌት ከእንግሊዛዊው ይለያል፡፡ እንደ ተዋናዩ የአተረጓጐም ብቃት … ገፀ ባህሪውን የመረዳት … ወይንም ወደ አካል ቋንቋ ቀይሮ የማቅረብ አቅም፡፡ የስብሐትም ሁኔታ ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡
“If Hamlet has something of the definiteness of a work of art, he has also all the obscurity that belongs to life. There are as many Hamlets as there are melancholies.” (The critic as Artist)
“አምስት ስድስት ሰባት” ላይ ያለው ድህነት … የስብሐት አይደለም፡፡ በፅሁፍ ላይ የሰፈረው ገፀ-ባህሪ የኢትዮጵያዊ ሁሉ ነው፡፡ የገፀ ባህሪውንም፤ ገፅ እና ባህሪ ደራሲው የሚስለው እኮ አንባቢው ልቦና ውስጥ ነው፡፡ … አንባቢ እኮ በፈጠራው ስራ ላይ ከግማሽ በላይ ባለቤት ነው፡፡ ደራሲው የሚፅፈው በሰዎች ልቦና ላይ ነው፡፡ “አምስት ስድስት ሰባት” ላይ ያለው ድህነት የእናንተ ነው፡፡ ስብሐት የሚባል ሰው ከእንግዲህ የለም … እረፉት!” ስብሐት አለ፤ ወንጀለኛ ወይንም ጠንቅ ነው… ብለን ስንወነጅለው እንኑር የምትሉ ከሆነ … እናንተ ናችሁ የሌላችሁት፡፡ የስብሐት ህይወት ላይ የምታነሱት የግብረ ገብ ጥያቄ … መቅረብ ያለበት … ለእናንተ ነው፤ ለእሱ አይደለም። “ቢግ ብራዘር አፍሪካ” ላይ ተደረገ ለተባለው ነውር ተጠያቂው ስብሐት ሊሆን አይችልማ፡፡ እናንተው ናችሁ ተጠያቂ፡፡ ቤቲም ልትጠየቅ አትችልም … ቤቲ ገፀ ባህሪን ተላብሳ ተወነች፡፡ እናንተ ገፀ ባህሪውን ተላብሳችሁ ተመለከታችኋት፡፡ ገፀ ባህሪውን ተላብሳችሁ ስብሐትን እንዲፅፋችሁ ወሰወሳችሁት። እሱ ለመፃፍ የተወሰወሰውን ያህል እናንተ ለማንበብ ተወስውሳችኋል፡፡ በሱ ውስጥ የምታነቡት ራሳችሁን ነዋ!
ስለዚህ ስብሐት ስንት መልክ አለው? ከተባለ … እኔ የምመልሰው “የእናንተን መልክ ብዛት” ብዬ ነው፡፡ ስብሐት ከስንት ብሔር መጣ? እናንተ ከመጣችሁበት የብሔር አማራጭ፡፡ ከስንት ማህፀን? እናንተን ካማጣችሁ የማህፀን ዥንጉርጉርነት … ወዘተ፡፡ ግን ተመልሼ ደግሞ ተጠራጠርኩ … ዥንጉርጉር ቢሆን ኖሮማ አመጣጣችሁ፤ ከሁለት አይነት የዕይታ አማራጭ ውጭ በተመለከታችሁ ነበር፡፡ ስብሐትን ወደ ልቅ ወሲብ አባትነት እና ልቅ የነፃነት ተሟጋች ከፍላችሁ ቁጭ አትሉም ነበር፡፡
… ከሁለት አማራጭ በላይ ያለ ለማስመሰል … በሁለት ድምፅ ደጋግሞ ለመዘመር … በየሳምንቱ ብዕር እና መርዝ እየቀላቀላችሁ የምታጠጡን ለምንድነው? … ብዕር በሽቶም ሆነ በመርዝ ቢሞላ ለስብሐት አይጠቅመውም፡፡ አይጐዳውም፡፡ ጉዳቱም ሆነ ጥቅሙ ለእናንተው ለራሳችሁ ነው፡፡ እንዲያውም ምን ጉዳት አለው? … ጥቅም ብቻ ነው። ግን ጥቅሙ “በስብሐት ላይ ተከራከርኩ!” ለማለት ያህል ብቻ ነው … በስብሐት ላይ ተከራከርኩ … ከሚሉት የበለጠ ደግሞ “አከራከርኳቸው!” የሚሉት የበለጠ ትርፍ ያገኛሉ፡፡ ስብሐት ቢወገዝም ሆነ ቢሞገስ የመፅሐፉ ሽያጭ ከፍ እያለ ይሄዳል፡፡ “ሰላዩ ተያዘ” ወይንም “ሰላዩ አመለጠ” የሚለውን ዜና የሚያትሙ መፅሔቶች በሁለቱም ረገድ ብዙ ኮፒ ይሸጣሉ፡፡ “The spy catcher effect” እያሉ ይጠሩታል፡፡ win win situation…ነው፡፡
እንጂማ፤ ስብሐትን የሚከተሉ ሰዎች በህገ መንግስቱ የህግ ከለላ አይነፈጋቸውም፡፡ በቤተ ክርስቲያኑም ፍትሀት አይከለክላቸውም፡፡ የስነ ምግባር አስተሳሰባችን ከመሰረቱ በተነቃነቀበት የወቅቱ ትውልድ ላይ … ደራሲውን በስነ ምግባር ለመክሰስ መሞከር … ከራስ ጋር ፍልሚያ ውስጥ መግባት ነው፡፡
በራችንን ለውጭው አለም ተፅኖዎች ከፍተን፣ ግን ዘግተን ለመቀመጥ የምንሞክረው በር፤ ምንም አይነት የስነ-ልቦና መሀንዲስ (ለበሩ) ማጠፊያ… ለክርክራችሁ ደግሞ ማጣፊያ መፍትሔ ሊሰጣችሁ አይችልም፡፡ ስብሐት … በመስታወት የማይታየውን ማንነታችንን አውጥቶ … አሳየን፡፡ በተፈጥሮአዊነት የአፃፃፍ ዘዴ ተጨባጩን ሲያሳየን ወነጀልነው፡፡ … ተፈጥሮአዊነትን ትቶ የሀያ አንደኛውን ክፍለ ዘመን የአፃፃፍ ዘይቤዎች … ሱሪያሊዝምም … ሆነ ፋንተሲ … መጻፍ ሲጀምርም ወነጀልነው፡፡ በተፈጥሮአዊነት ተፈጥሮአችንን ስላሳየን ወነጀልነው፡፡ በምናባዊ የአፃፃፍ ዘይቤ ተፈጥሮአችንን “ሮማንቲሳይዝ” አድርጐ ሳያሳየን ሲቀርም ወንጀል ሆነ፡፡ “The nineteenth century dislike of Realism is the rage of caliban seeing his own face in the glass. The nineteenth century dislike of Romanticism is the rage of caliban not seeing his own face in a glass” (The Picture of DNIAN GRAY) ለምን ታሳየናለህ? … እና ለምን አላሳየኸንም? የሚለውን ግራ የተጋባ ጥያቄ መመለስ የሚችለው … ምን ማየት እና አለማየት እንደሚፈልግ የሚያውቅ ሰው ብቻ ነው፡፡ ይህንን መምረጥ የሚችል ሰው ደግሞ ራሱ ደራሲ ነው። ተራ አንባቢ የተሰጠውን መቀበል የተጣለበት ፍርጃ ነው፡፡ ተቀብሎ ሲያበቃ “አልቀበልም” የሚል ድንፋታ የትም አያደርስም … ጋዜጣ ላይ ስምን አትሞ ከማስነበብ በሚገኝ “በህይወት አለሁ ለካ!” የጉራ ባዶነት ውስጥ ከመሳከር በስተቀር፡፡

Published in ጥበብ
Saturday, 24 August 2013 11:31

እዚያው ሁን ግዴለም!

ሰሌ…
አገርህ ያችው ናት፤
ዛሬም ልባም የላት፡፡
የድሀ አገር ህዝቦች፣ ህልማቸው አንድ ነው
ራዕይ ይሉታል፣ ቅዠቱን ደራርተው፡፡
አምኜ ፃፍኩልህ፣ ግጥም የነብስህ ነው፡፡
እዚያው ሁን ግዴለም፤ እዚያው አጣጥመው፡፡
ሰሌ………..
“አንድ ዓመት አለፈ
አንድ ዓመት አረፈ”
አልንህ ተሰብስበን፤
ባንድ ሻማ ጉልበት፣ እኛ አንድ ዓመት ኖረን፡፡

አንድ ዓመት፣ ብዙ ቀን፣ ይመስለኝ ነበረ
አንድ ዓመት ሩቅ ቀን፤ ይመስለኝ ነበረ
ግን አሁን ሳሰላው
ተቀጭቶ ከቀረ፣ በዚያ ዓመት አንድ ሰው
ለካ አንድ ዓመት ማለት፣ አንድ ዕምቅ አፍታ ነው፡፡
ሰሌ…
እንዳላለቀ ፊልም
እንዳልጨረሱት ህልም
እንዳልቋጩት ፍቅር
ትዝ ትለኛለህ፡፡
እና ዛሬም አለህ፡፡
አልፏል እልህና
የማለፍን ትርጉም ታስጠፋብኛለህ፡፡
አይበቃኝም ቃሉ፣ ትዝታ እንዳልልህ
ምንም ነህ ሁሉም ነህ
ዛሬም ትስቃለህ …
ዛሬም ታሾፋለህ…
ዛሬም ብቻህን ነህ…
ግን እኛ ውስጥ አለህ!!
እንዴት ነው ትዝታ፣ አንተን እሚገልጽህ?
ሰው ትንግርቱ አያልቅም
ምኑ እንደሚማርክ ፣ ምክኑ አይታወቅም፤
ኪኑ አይገለጥም፡፡
አለው ብርቱ ውበት፣ አለው ብርቱ ህመም
ክፉም ክፉ አደለም፣ ደግሞ ደግ አደለም
እንደዚያ ነህ አንተም፡፡
ሰሌ …
አንዳንዴ አገር ማለት፣ ዕንቆቅልሽ አደል?
ጨካኝ - ተጨካኙ፣ አንድ ላይ ይኖራል፡፡
ያው እንደምታውቀው፣ መብራቱም ይጠፋል
ያው እንደምታውቀው፤ ባምቧውም ይደርቃል
ያው አምና እንዳየኸው፤ ስልኩም መስመር የለው፡፡
ንገር ጐንህ ካለ የሚመለከተው - አገር የመራ ሰው፡፡
ከነሙስናችን …
ከነብዥታችን…
ከነብሶታችን…
የሞትነውን ያህል፣ ኖረናል እያልን፤
እዚያው ቁጭ ብለናል፣ ያው እንዳስቀመጥከን፡፡
ሰሌ….
ዝም ብለህ ተኛ እዚያው፣ ለዓለም ለዘለዓለም
ያየኸው ነው ያለው፣ ካምናው ሌላ የለም፡፡
ንብረት ተዟዙሯል፣ ሰው አልተሻሻለም፤
በዕድሜ ማርጀት እንጂ፣ ልምላሜ የለም፤
ቀኑ ተገፋ እንጂ፣ ኑሮ አልተለወጠም
ውሃው ሊገድብ ነው፣ ኑሮ አልተገደበም፡፡
ሰሌ…
የእኛ ችግኝማ፣ ምኔም ሰው ነውና
በጐራ ወይ በጐጥ፣ ስለማንፈርጀው
ያንተ መታሰቢያ፣ ልባችን ብቻ ነው
ልብ ያነባ እንደሆን፣ የዕንባ ወንዙን እየው!
ዛሬም አብረኸን ነህ፣ እዚያው ሁን ጉድ የለም፡፡
ቀኑን ገፋን እንጂ ኑሮ አልተለወጠም
የነገን እንጃልን፣ ተስፋ ግን አይሞትም!!
ነሐሴ 15 2005 ዓ.ም
(ለሰለሞን ጐሣዬ ሙት ዓመት፣ ለቤተሰቡና ለካዛንቺስ ወዳጆቹ)
(የሰለሞን ጐሣዬን ሙት ዓመት ለማክበር፤ የጧፍ ማብራትና
የነብስ ይማር ሥነስርዓት አከባበር ላይ ለተገኛችሁ የካዛንቺስ አካባቢ ወዳጆቹ ልባዊ ምሥጋና ይድረሳችሁ!)

Published in ጥበብ
Saturday, 24 August 2013 11:28

ሰላሳ ምናምነኛው ጋጋታ

      በቅርቡ “መልክአ ስብሃት፤ ስብሃት ገብረእግዚአብሔር በሰላሳ ፀሐፊያን፤ ገጣሚያን እና ሰዐሊያን እይታ” የምትል መፅሀፍ በአለማየሁ ገላጋይ አርታኢነት ታትማለች፤ አርታኢው በመጽሐፉ ጀርባ ላይ እንዲህ ብሎ ጽፏል፡- “ሠላሳ ያህል ፀሐፊያን፣ ገጣሚያንና ሰዐሊያን ስለስብሀት ገብረእግዚአብሔር ያላቸውን የተለያየ አመለካከት በአንድ ላይ አጣምረው በዚህ መድበል አቅርበዋል፡፡ ሥራው ለሥነ-ፅሑፋዊም ሆነ ለማህበራዊ ሂስ በአዲስነትና በበር ከፋችነት የሚጠቀስ ለመሆኑ አያጠራጥርም፡፡”
መልካም፡፡
ተስማምተናል፡፡
ይህ አዲስ እና የመጀመሪያው “መልክአ…” ስለሆነ (መልክአ ፀጋዬ፣ መልክአ በዐሉ፣ መልክአ አዳም ይኖራል ተብለናል) እንዴት መፃፍ እንዳለበት፣ ቅርጹ እና ይዘቱ ምን መሆን እንዳለበት የታወቀ ነገር ያለ አይመስለንም፡፡ ለምሳሌ፣ የአስፋው ዳምጤ ፅሁፍ ለምን መጀመሪያ፣ የፀደይ ወንድሙ ፅሁፍ ለምን መጨረሻ ላይ እንደቀረበ ምንም የተባለ ነገር የለም፡፡ ለካርቱኖቹ ማውጫ የላቸውም፤ ካርቱኖቹ የገቡበት ገጽ ላይ ለምን እንደገቡ አናውቅም፡፡ ለረዥም ዘመን የስብሃት መለያ የነበረውና የእግረመንገድ አምድ ጽሁፎቹን የሚያጅበው የማህሌት ወርቁ ካርቱን ለምን እንዳልተካተተም ገርሞናል፡፡ የወደድናት ካርቱን፣ ገጽ 263 ላይ ስብሃት ከሚወረወሩበት ጦሮች አንዷን ሲጋልብ የምታሳየው ናት፤ ድንቅ ብለናል፡፡
ከይዘት አንፃር አራት ህፀጾችን እንጠቅሳለን፡፡
የሌሊሳ ስህተት
የከበደ ስህተት
የአዳም ስህተት
የአውግቸው ስህተት
የሌሊሳ ስህተት
ሌሊሳ ግርማ “ስብሃት እና ሄሚንግዌይ አንድ ናቸው” በሚለው ፅሁፉ እንዲህ እያለ ያመሳስላቸዋል “ስብሃት የተወለደው አድዋ ነው፤ ሄሚንግዌይ ደግሞ ኦክፓርክ (ኤሊኖይ)፡፡ ሄሚንግዌይ በ 1899 እ.ኤ.አ. ነው የተወለደው፣ ስብሃት ደግሞ በአበሻ አቆጣጠር 1929 … ሁለቱም በተወለዱበት ዓመት ላይ ሁለት ዘጠኝ ቁጥሮች አሉባቸው፡፡ ስለዚህ አንድ ናቸው፡፡…” ተው እንጂ! እሺ 1899 እና 1929 በሁለት ዘጠኞች ይመሳሰሉ፡፡ አድዋ እና ኦክፓርክ (ኤሊኖይ) በምን ይመስላሉ? “አ ፊደል እና የአ ፊደል ዝርያ ስላላቸው ነዋ!” ሳይለን አይቀርም ብራቮ ልጅ፤ አሪፍ አዛምድ ነው ባክህ! “አይ ሌሊሳ ሲቀልድ ነው” ልንባል ይችል ይሆናል፡፡ እሱም እንዲያ አስመስሏል፡፡ እንዲያውም፡- “ይቅርታ! አሁን ወደ ቁምነገሩ ልምጣ…” በማለት በቀጥታ ወደ “ቁም ነገሩ” የሚመጣው እንዲህ እያለ ነው፡- “የሁለቱም ደራሲዎች ህይወት አልፏል፤… የሁለቱም ፊት በነጭ ፂም የተሸፈነ ነው…” ይሄ ነው ቁምነገሩ፡፡ ምን እየተባልን ነው? የሞቱና ፊታቸው በነጭ ፂም የተሸፈነ ደራሲዎች ሁሉ ይመሳሰላሉ? ኤድያ! አቦ ተዉና! “ስብሃትና ሄሚንግዌይ አንድ ናቸው” የሚል፤ “ እስኪ፣ እስኪ፣ እንዴት፣ እንዴት …” የሚል ጉጉት የሚፈጥር ርዕስ ይዞ ተነስቶ፣ በዘጠኝ ቁጥር፣ በሞት እና በፂም አንድ ናቸው ብሎ ነገር ምን ይሉት ማመሳሰል ነው?! መድበሉ ውስጥ ከተካተቱት ጽሁፎች አጭሩ የሌሊሳ ነው፡- እንኳንም አጠረ፡፡ ቢረዝም ሌላ ረዥም ስህተት ይጽፍ ነበር፡፡ ከላይ ያሉትን እንደምሳሌ ጠቀስን እንጂ ሌሎችም ማመሳሰያዎቹም ስህተት ናቸው፡፡ ሄሚንግዌይ ለቦክሰኛ አገዘ፣ ስብሃት ለዘፋኝ (ዘሪቱ) አገዘ፤ ስለዚህ አንድ ናቸው” ብሎ ማመሳሰል ምን ይሉት ነው?
የከበደ ስህተት
“ህያው ስብሃት” የሚል ርዕስ ያለው የከበደ ደበሌ ሮቢ ፅሁፍ እንዲህ ሲል ነው የሚጀምረው፡- “The Seventh Seal (ሰባተኛው ማህተም) የዝነኛው ስዊዲናዊ ደራሲ(?) ኢንግማን በርግማን መፅሀፍ (??) ርዕስ ነው፡፡” ውዲ አለን “ሁሉን አስተውለን ስንዳኝ፣ ኢንግማን በርግማን የሲኒማ ካሜራ ከተፈለሰፈ ወዲህ ከተፈጠሩ የፊልም ባለሙያዎች ታላቁ ነው፡፡” ያለለት የፊልም ፀሀፊ፣ ፕሮዲዩሰር እና ዳይሬክተር ነው - ኢንግማን በርግማን፡፡ ከበደ ሊጠቁም እንደሞከረው የልብ ወለድ ፀሀፊ አይደለም፤ The Seventh Sealም መፅሀፍ አይደለም፤ ፊልም ነው፡፡ ወይስ ከበደ ደበሌ ሮቢ መጽሐፍ ያያል፤ ፊልም ያነባል ሊባል ነው?
የአዳም ስህተት
“የዛሬ ድርጊት ትናንትናና ነገ በትውስታ የሚያያዙበት ነው፡፡” ብሎ የሚጀምረው አዳም ረታ፤ “የስብሃት ተረቶች ትዝታ” በሚል ርዕስ የቀረበ ነው፡፡ ፅሁፍ ስብሃትን “የማያፍር አስታዋሽ ነበር” ብሎ አሞግሶታል፡፡ የአዳም ፅሁፍ ከሌሎች ይለያል፡፡ ፍልስፍናዊ ነው፡፡ “ያለፉት በእርግጥ አልፈዋል” በሚል ጀምሮ፣ “ያለፉት በእርግጥ አልፈዋል?” ብሎ የሚያበቃ አሪፍ ፅሑፍ ነው፡፡ (ልዩነቱን ልብ ይሏል፡፡) ይህ ሰውም ግን የማትታለፍ ስህተት ፅፏል፡- “ከብዙ አስደሳች(?) አጫጭር ታሪኮቹ ሞፖሳ በ “ዘ ጊፍት ኦፍ ዘ ሜጃይ ትዝ ቢለን ከስርዓት አልወጣንም፡፡” ይላል አዳም፡፡ The Gift of the Magi የ ኦ ሄነሪ አጭር ልብ ወለድ ናት፡፡ ለምሳሌ፡- “ከብዙ አስደሳች አጫጭር ታሪኮቹ ከሰማይ የወረደ ፍርፍር ደራሲ ስብሃት ገብረእግዚሀብሄር ትዝ ቢለን ከስርዓት አልወጣንም፤ ወይም ከብዙ አሳዛኝ አጫጭር ታሪኮቹ የአምስት ስድስት ሰባት ደራሲ አዳም ረታ ትዝ ቢለን ከስርዓት አልወጣንም፡፡” የሚል አይነት ስህተት ብንሰራ አዳም የሚደብረው ይመስለናል፡፡ ይደብራል፡፡
የአውግቸው ስህተት
የአውግቸው ተረፈን ስህተት ምን ብለን እንደምንጠራው አላወቅንም፡፡ አውግቸው ለምን እንደፃፈው፣ አርታኢው ለምን ነቅሶ እንዳላስቀረው አልገባንም፡፡ ያለቦታው የገባ በጣም የሚያስጠላ የቂም አስተያየት ነው፡፡ አንብበነው ቀፈፈን፡፡ አውግቸውን ከጽሁፍ ስራዎቹ በተጨማሪ በጣም ያወቅነውና የወደድነው፣ ስንዱ አበበ በተናገረችው ነገር ነው፡፡ የሆነ ቃለ መጠይቅ ላይ ስለ አውግቸው ስታወራ፡- “እብደት ውስጥ እያለ ሌሎች ያንን እንዲያውቁ ስለእብደት መጽሀፍ ከመጻፍ የላቀ ደግነት የለም፡፡” ብላ ነበር፡፡
አውግቸው ስለባሴ ሀብቴ የፃፈውን እንዲህ እንደወረደ እንጠቅሳለን፡- “ያኔ እኔ የመንፈስ ጭንቀት አደረብኝና የኩራዝ መስሪያ ቤትን በገዛ ፈቃዴ ለቅቄ ወጣሁ፡፡ በየጠቅላይ ግዛቶቹም እዞር ጀመር፡፡ ደሴ፣ አሰብ፣ ድሬዳዋ፣ አርሲ፣ አዋሳ፣ ሻሸመኔ፣ ዲላ፣ መተከል፣ ደብረማርቆስ… አካልዬ ከተመለስኩ በኋላ ያጐቴ ልጅ አማኑኤል ሆስፒታል ወስዶ አስገባኝ፡፡ ከዚያ በደንብ ሳልታከም ጠፍቼ ወጣሁ፡፡ ያኔ ወደ አሮጌ መጽሐፍ ተራ እሄድ ነበር፡፡ ባሴ ሀብቴም “ውሽንፍር” እና ቃል የተባሉትን የትርጉም ስራዎች የመጽሐፍ ተራ ነጋዴዎች አሳትመውለት ከ “ውሽንፍር” አስር ሺህ ብር፣ ከ“ቃል” ሶስት ሺህ ብር አግኝቶ ስለነበር ከመጽሐፍ ተራ አይለይም ነበር፡፡
ያኔ የመጽሐፍ ተራ ሰዎች የኔን መታመም እና ጩቤ እየያዝኩ መዞር አይተው፣ ጩቤውን አስጥለው ወደ አማኑኤል ሆስፒታል ሊወስዱኝ ከእኔ ጋር ሲታገሉ “ተዉት፣ ልቀቁት ይሂድ፡፡ እሱ ሰሞኑን ሟች ነው” ብሎ ተናገራቸው፡፡ የመጽሐፍ ተራ ሰዎች ግን የሱን ቃል ሳይሰሙ እኔን ወደ አማኑኤል ሆስፒታል ወስደው አሳከሙ፡፡ እኔ ይኸው እስካሁን አለሁ፡፡ እሱ ግን ዘላለም ኗሪ መስሎ የነበረው ከኔ ቀድሞ ሞተ፡፡ ባሴ ማለት ከእኔ ጋር በአንድ ቤት ውስጥ ለስድስት ዓመታት አብሮኝ የኖረ ነው፡፡ ከአቶ ስብሃት ጋርም ያስተዋወቅሁት እኔ ነበርኩ፡፡”
ለህይወት እና ለሰው ምርጥ ፍቅር ስለነበረው ሰው (ስለ ስብሃት) የሚጽፍ ሰው፣ ከሞተ ከ 10 ዓመት በላይ ስለሆነው ባሴ ሃብቴ እንዲህ ያለቦታው የሻገተ ቂም ሲጽፍ፣ አስቀያሚ ስህተት ነው ከማለት ሌላ ምን እንላለን? (በነገራችን ላይ ነፍሱን ይማረውና ደምሴ ጽጌ እራሱ ባሴ ሃብቴ በሞተበት ዓመት አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ እንዲህ አይነት ቀፋፊ ጽሁፍ ጽፎ ነበር፡፡)
የአውግቸው ተረፈ ርዕስ “እኔና አቶ ስብሃት” ነው የሚለው፡፡
እኛ፣ አንዳንዶቹን ፅሑፎች ስናያቸው ፀሐፊዎቹ ስብሃትን ከራሳቸው አንፃር ያዩበትና ያሳዩበት ሳይሆን እራሳቸውን ከስብሃት አንጻር ለማየትና ለማሳየት የታተሩበት ነው፤ ባፈጠጠ ሁኔታ፡፡ ምን ያህል ያፈጠጠና ያገጠጠ መሆኑን የፀሐፊዎቹን ፅሑፍ እየጠቀስን እናሳያችኋለን፡፡ (ዋናውን ቁም ነገር በሚቀጥለው ሳምንት)

Published in ጥበብ

ዋና ሳጅን ገረመው ታደሰ ይባላል፡፡ በፌደራል ፖሊስ ኢንጅነሪንግ ዲፓርትመንት ውስጥ በምህንድስና ሙያ ይሰራል፡፡ ኮሜንታተርም ነው፡፡ በትርፍ ሰዓቱ የእግር ኳስ ጨዋታዎችን በሞባይሉ ለአርባ ምንጭ ስፖርት አፍቃሪዎች ያስተላልፋል፡፡ የፈጠራ ሃሳቡ የራሱ ነው፡፡ ዋና ሳጅን ገረመው በኮሜንታተርነቱ ባገኘው አድናቆት የአርባ ምንጭ ከነማ የእግር ኳስ ክለብ የህዝብ ግንኙነት ሥራዎችን እንዲሰራ ተደርጓል። የስፖርት አድማስ አዘጋጅ ግሩም ሰይፉ፤ ባለትዳርና የ4 ልጆች አባት ከሆነው ዋና ሳጅን ገረመው ጋር እንደሚከተለው አውግቷል፡፡
እኔ የማውቅህ በኮሜንታተርነት ነው፡፡ እስቲ ስለምህንድስናው ንገረኝ?...
በፌደራል ፖሊስ የምህንድስና ክፍል ባለሙያ ነኝ፡፡ በምህንድስና ሙያዬ በተለያዩ የኮንስትራክሽን ስራዎች በህንፃ ፎርማንነት እያገለገልኩ ነው፡፡ በዚህ ሃላፊነቴ በትልቅ ፕሮጀክት ላይ እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡ ፕሮጀክቱ በኮልፌ የሚገኘው የፌደራል ፖሊስ አባላት የመኖርያ ካምፕ ነው፡፡
ዋና ሙያህና ኮሜንታተርነቱ አይጋጭብህም?
የክፍል አባሎቼ ለስፖርቱ ያለኝን ከፍተኛ ፍላጎት እና ዝንባሌ ያውቃሉ፡፡ ትልቅ ደረጃ እንድደርስ ስለሚመኙ ሁሌም ድጋፍ ያደርጉልኛል፡፡ በዚህም ምስጋና ይገባቸዋል፡፡ በተረፈ ግን ብዙ ጊዜ፤ ኮሜንታተርነቱን በእረፍት ሰዓቴ ነው የምሰራው፡፡ እንደምታውቀው የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች የሚካሄዱት ከ10 ሰዓት በኋላ ነው፡፡ ብዙ ጨዋታዎችም ቅዳሜ እና እሁድ ነው የሚደረጉት፡፡ እናም ሁለቱ ሥራዎች የሚጋጩበት ሁኔታ የለም፡፡ እስካሁንም ምንም ችግር ሳይገጥመኝ ሁለቱንም በሙሉ አቅም እና ብቃት ጎን ለጎን እያካሄድኩ ነው፡፡
እንዴት ነው ወደ ኮሜንታተርነት የገባኸው?
ኮሜንታተር የሆንኩት ለእግር ኳስ ባለኝ ከፍተኛ ፍቅር ነው፡፡ በተለይ የደምሴ ዳምጤን አርዓያ ለመከተል ፍላጎት ነበረኝ፡፡ ደምሴ ዳምጤ በጣም የማደንቀው ኮሜንታተር ነበር፡፡ ጨዋታዎችን በቀጥታ የሚያስተላልፍበት መንገድ፤ የሚሰጠው መረጃ፣ የአገላለፅ ችሎታው ፤ የእግር ኳስ ስሜቱ እና ድምፁ ሁሉ ያስደስተኛል፡፡ ይገርምሃል ደምሴ ዳምጤ በኮሜንታተርነት የሚያስተላልፈውን ጨዋታ ለመስማትና ለማየት ብዬ ለእስር ተዳርጌአለሁ፡፡ የዛሬ 26 ዓመት ነው፡፡ ኢትዮጵያ፤ የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ውድድርን አዘጋጅ ነበረች፡፡ ያኔ እኔ ለምረቃ እየተዘጋጀሁ ያለው ምልምል ፖሊስ ነበርኩ፡፡ ፖሊስ ለመሆን አንድ አመት ከሁለት ወር በለገዳዲ የፖሊስ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት መሰልጠን ያስፈልጋል፡፡ አንድ ወሩ ግን የልምምድ ጊዜ ነው፡፡ እኔ እና ሌሎች ባልደረቦቼ ለመመረቅ የልምምድ ስራ ላይ ነበርን፡፡ እንዳጋጣሚ ሆኖ የተመደብነው ደግሞ ስቴዲየም ነው፡፡ ክፋቱ ግን እኔ የነበርኩት ውጭ ነው፤ 7 ቁጥር በር አካባቢ፡፡ በጣም አዘንኩ፤ አለቀስኩ፡፡ ጓደኞቼ እንዲቀይሩኝ ጠየቅኋቸው፡፡ እነሱም ጨዋታውን መመልከት ስለፈለጉ ፈቃደኞች አልነበሩም፡፡ ከዚያ ምን አደረግሁ መሰለህ? የተመደብኩበትን ስራ ትቼ ጂንስ ጃኬት አስመጣሁና ለብሼ ወደ ስታዲየም ውስጥ በመግባት፣ ህዝብ መሃል ቁጭ አልኩ፡፡ በካታንጋ በኩል ነበር፡፡ አለቃዬ ፈልገውኝ ስታዲየም መግባቴን ሲሰሙ ስሜ እንዲመዘገብ አደረጉ፡፡ እኔ ግን ደስ ብሎኛል፡፡ የተመደብኩበትን ሥራ ጥዬ ስቴዲየም በመግባቴ ምን እንደሚከተለኝ እንኳ አላሰብኩም፡፡
ጨዋታው ተጀመረ፡፡ እዚያው ካታንጋ መሃል ከጎኔ የነበረ አንድ ሰውዬ ትንሽዬ ሬድዮ ይዞ ነበር፤ “ስጠኝ” አልኩት፤ ሰጠኝ፡፡ ጨዋታውን እያየሁ በሬድዮ ደምሴ ጨዋታውን ሲያስተላልፍ፣ ለመስማት ፈልጌ ነው፡፡ ደምሴ የብሔራዊ ቡድናችንን ብርቅዬ ተጨዋቾች አሰላለፍ በሬዲዮ ሲያስተላልፍ በዓይኔ መመልከቴ ልዩ ስሜት ፈጠረብኝ፡፡ ከዚያች ቀን ጀምሮ ነው ኮሜንታተር ለመሆን የወሰንኩት፡፡ ቤቴ ውስጥ ቁጭ ብዬ ድምፄን እየቀዳሁ ኮሜንታተር ለመሆን መለማመመድ ጀመርኩ፡፡ ያደረግሁትን ሁሉ ለጓደኞቼ እነግራቸው ነበር፡፡ ድምፄንም ሲሰሙ ጥሩ ነው ብለው አበረታቱኝ፡፡ በዚያው ቀጠልኩበት፡፡
አለቃህ ምን አሉ… ስቴዲዬም በመግባትህ?
አለቃዬ ሲጠይቁኝ፤ “ጌታዬ፤ ስሜቴን መቆጣጠር አልቻልኩም፤ ጨዋታውን ማየት ነበረብኝ፡፡ ጓደኞቼን ቀይሩኝ ብላቸው እምቢ ሲሉኝ ነው የገባሁት” አልኳቸው፡፡ ጥፋተኛ ነህ ተብዬ ኮልፌ ለአምስት ቀን ታሰርኩ፡፡ የሚገርምህ ከደምሴ ብዙ ተምርያለሁ፡፡ ዋናው ነገር ግን አንድ ሰው ለ90 ደቂቃ ጨዋታውን በተሟላ አቅም እና በሚያጓጓ ስሜት ተከታትሎ ማስተላለፍ እንደሚችል ማወቄ ነው፡፡ ደምሴን የማደንቀው በዚህ ነው፡፡ ለ90 ደቂቃ ጨዋታ ማስተላለፍ የለመድኩትም ከሱ በወሰድኩት አርዓያነት ነው፡፡ ከ65 ደቂቃ በኋላ ማንኛውንም ጨዋታ ስታስተላልፍ ይደክምሃል፡፡ ድምፅህ ሃይሉ ሊቀንስ ይችላል፡፡ እኔ ግን በልምምድ ጨዋታዎች 90 ደቂቃ ሙሉ ለብቻዬ የማስተላለፍ ብቃት አዳብሬያለሁ፡፡ ጨዋታዎችን በማስተላለፍበት ጊዜ አንድ በእግር ኳስ ህይወት እንግዳ ይኖረኛል፡፡ በተለይ ከደቡብ ክልል የሆነ ስፖርተኛ አቀርባለሁ፡፡
የአርባምንጭ ክለብ ኮሜንታተርነትን እንዴት እንደጀመርከው ንገረኝ…
በአንድ ወቅት ከአርባ ምንጭ እግር ኳስ ክለብ አመራሮች ጋር ሆነን የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የአርባምንጭ ጨዋታን ለማስተላለፍ ፈለግን፡፡ የአርባምንጭ ስፖርት አፍቃሪ ክለቡ በአዲስ አበባ የሚያደርገው ጨዋታ እንዲተላለፍለት ጠይቆ ነበር፡፡ እኔ ደግሞ የአርባምንጭ ደጋፊዎች የአዲስ አበባ አስተባባሪ ስለነበርኩ፣ ከክለቡ ሃላፊዎች ጋር ሆነን በዛሚ ኤፍኤም ጨዋታውን በቀጥታ ለማስተላለፍ ጠየቅን፡፡ የተጠየቅነው ገንዘብ ከፍተኛ ነው -13ሺ ብር፡፡ ያልጠበቅነው ነበር፡፡
የክለቡ አመራሮች “ሳጅን ምን ታስባለህ” አሉኝ። እኔ ይሄ ሁሉ ገንዘብ ሊከፈል አይገባም አልኳቸው። ከዛም ጨዋታውን ማስተላለፍ የምችልበት ዘዴ እንዳለኝ ገለፅኩላቸው፡፡ “እንዴት አድርገህ” አሉኝ፡፡ አርባምንጭ ከምታውቁት ሙዚቃ ቤት ጋር አገናኙኝ አልኳቸው፡፡ ቀደም ሲል ጨዋታውን ስታዲየም ሆኜ በስልክ ማስተላለፍ እንደሚቻል ያደረግኋቸው ሙከራዎች ነበሩ፡፡ ስለዚህ ነገሩ እንደሚሳካ ጥርጥር አልነበረኝም፡፡ ኖኪያ የስልክ ቀፎ አለኝ፤ በሄድፎን ጆሮዬ ላይ እሰካዋለሁ፡፡ ከዚያም አርባምንጭ ከተማ ከሚገኘው ሙዚቃ ቤት ጋር በቀጥታ ስልክ በመደወል እገናኛለሁ፡፡ ሙዚቃ ቤቱ በስልኩ የማስተላልፈውን የእኔን ድምፅ በጃክ በመቀጠል በሞንታርጎ ያሳልፈዋል። እናም “ብርሃን ፀረ ኤድስ ማህበር” ከሚባል ሙዚቃ ቤት ጋር በመተባበር ጨዋታዎችን ማስተላለፍ ጀመርኩ - በኮሜንታተርነት ነው፡፡ የማህበሩ ፕሬዝዳንት አቶ በረከት አርባምንጭ ሆነው በቴክኒክ ተቆጣጣሪነት ይሰሩልኛል፡፡
ስፖርት አፍቃሪው የት ሆኖ ነው ጨዋታውን የሚከታተለው?
ጨዋታው በአርባምንጭ መናኸርያ ነው የሚተላለፈው፡፡ መናኸርያው በጣም ሰፊ ነው። በዚያው አካባቢ አምስትና እና ስድስት ሞንታርጎ ስፒከሮች በ4 ሜትር ልዩነት ተራርቀው በተለያዩ አቅጣጫዎች ይቀመጣሉ፡፡
ጨዋታውን ስታስተላልፍ ምን ያህል ሰው ይከታተልሃል?
ስጀምር በአንድ ጨዋታ እስከ 20ሺ ሰው ይከታተለኝ ነበር፡፡ አሁን እስከ 30ሺ የሚደርስ ይመስለኛል፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ ያስተላለፍኩት ጨዋታ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና አርባምንጭ ያደረጉት ነበር፡፡
“አድማጮቻችን መስመራችን ከአሁን ሰዓት ጀምሮ በቀጥታ ከአዲስ አበባ ስታዲየም 505 ኪሎ ሜትር ተጉዞ አርባምንጭ ከተማ ይደርሳል። በዛሬው እለት በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ 26ኛ ሳምንት፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የአርባምንጭ ከነማ ጨዋታን እናስተላልፋለን፡፡ አሁን የአርባምንጭ ከተማ አሰላለፍ ደርሶኛል፤ እንደሚከተለው እገልፃለሁ፡፡ 1 አንተነህ መሳይ፤ 2 አንተነህ ተስፋዬ፤ 3 እምሻው ካሱ፤ 4 ታገል አበበ፤ 5 አብዮት ወንድይፍራው፤…” እያልኩ አስተዋውቃለሁ፡፡ በመጀመርያ የየክለቦቹን የተጨዋቾች አሰላለፍ ዝርዝር እገልፃለሁ፡፡ የተጨዋቾችን ስም ዝርዝር ከቡድን መሪዎች አገኛለሁ። የማላገኝ ሲሆን ከማሊያቸው እያየሁ አስተላልፋለሁ፡፡ የማውቃቸውን በስም እጠቅሳለሁ፡፡ ብዙ ጊዜ በግራ ጥላ ፎቅ፤ የጊዮርጊስ ደጋፊዎች በሚቀመጡበት አካባቢ ሆኜ ነው ጨዋታዎችን የማስተላልፈው፡፡
በደጋፊ መሃል ሆኖ ጨዋታውን ማስተላለፍ አይቸግርም? ለምን ለኮሜንታተሮች በተመደበው የትሪቡኑ ክፍል ወይም መሐል ሜዳ ትራኩ አካባቢ ወርደህ አታስተላልፍም?
ይህን ብዙ አላሳብኩበትም፡፡ ፌደሬሽኑ ካልከው ሥፍራ እንዳስተላልፍ ይፈቅድልኛል ብዬ አስባለሁ። የፌደሬሽኑ ሃላፊዎች የምሰራውን ስራ የሚያደንቁ ይመስለኛል፡፡ እስካሁን ማንም አልከለከለኝም፡፡ በፈጠራዬ ከብዙ አካላት አድናቆት አትርፌያለሁ። ጋዜጠኞች ስለእኔ ተግባር በአድናቆት ዘግበዋል ፅፈዋል፡፡ ለእኔም ከፍተኛ የሞራል ስንቅ ሆኖኛል፡፡ በአዲሱ የውድድር ዘመን ይህን ስራዬን እንዳልከው ፈቃድ አግኝቼ በትሪቡን ለመስራት ሃሳብ አለኝ፡፡ ኮሜንታተርነት ስሜታዊ ቢያደርግም ሚዛናዊ ሆነህ ጨዋታውን ማስተላለፍ አለብህ ብዬ አምናለሁ፡፡ በኮሜንታተርነቴ በአርባምንጭ በመደነቄ፣ የክለቡን የህዝብ ግንኙነት ስራዎች እንድሰራ አድርጎኛል፡፡ እስካሁን በስራዬ ያገኘሁት ሽልማት ባይኖርም ከህዝቡ የማገኘው ፍቅር ትልቅ ብርታት ነው፡፡
እስከዛሬ በዚህ መንገድ ስንት ጨዋታ አስተላለፍክ?
ሁለት ዓመት ሰርቼያለሁ፡፡ የአርባምንጭ ክለብ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ከሜዳው ውጭ የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች በሙሉ አስተላልፌያለሁ፡፡ ከአርባምንጭ ስታዲየም ደግሞ በአዲስ አበባ ኮልፌ ፤ ሽሮሜዳ እና አስኮ ለሚኖሩ የክለቡ ደጋፊዎች ለበርካታ ጊዜያት ጨዋታዎችን አስተላልፌያለሁ፡፡ በአዲስ አበባ 20ሺ የሚደርሱ የክለቡ ደጋፊዎች እንዳሉ እገምታለሁ፡፡ ከአርባምንጭ ስታዲየም የምንደግፈው ክለብ ጨዋታ ይተላለፍ ብለው ይጠይቁኛል፡፡ ዘንድሮ የአርባምንጭ ክለብ ካደረጋቸው ጨዋታዎች ውስጥ 18 ጨዋታዎችን ሰርቻለሁ፡፡ ከሜዳው ውጭ ያደረጋቸውን ሁሉንም 13 ጨዋታዎች አስተላልፌያለሁ፡፡ ካስተላለፍኳቸው ጨዋታዎች ምርጥ የምለው፣ የዘንድሮው ሻምፒዮን ደደቢት እና አርባምንጭ ተገናኝተው 1ለ1 የተለያዩበት ጨዋታ ነው፡፡
እስቲ ስለ አርባምንጭ ስታዲየም ንገረኝ…? የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች በርካታ ተመልካች ከሚያገኙባቸው የአገሪቱ ስታዲየሞች አንዱ ነው…
የአርባምንጭ ስታዲየዬም ተራራ አጠገብ ነው። ከተራራው ስር ሜዳው አለ፡፡ በጥላ ፎቁ በኩል እስከ 25 ሜትር ከፍ ባለው እና ወደ ጎን ረጅም በሆነው ጋራ እርከን ተሰርቶለታል፡፡ በኮረብታው ላይ በሲሚንቶ መቀመጫ ተሰርቷል፡፡ በካታንጋ በኩል ደግሞ በሽቦ ታጥሮ ተመልካች ይገባበታል፡፡ ብዙ ጨዋታዎች ሲደረጉ 70ሺ ያህል የስፖርት አፍቃሪ ይገኛል፡፡ በአንድ ጨዋታ በአማካይ እስከ 55ሺ ተመልካች አይጠፋም። 3ብር፤ 5ብር እና 10 ብር ነው መግቢያው፡፡ በርግጥ ሳይከፍል የሚገባም ይኖራል፡፡ ከፍሎ ባይገባም ከስታዲየሙ ክልል ራቅ ብሎ እስከ 15ሺ የሚደርስ ተመልካች ጨዋታውን ሲታደም ትመለከታለህ። እንዴት ደንበኛ ስታድዬም አልተሰራም ልትል ትችላለህ፡፡ በቅርቡ እንደሚገነባ አልጠራጠርም፡፡ አርባምንጭ ከነማ ክለብ፤ ፕሪሚዬር ሊግ በገባበት በዚህ አመት ይህን ተፈጥሯዊ ስታዲየም ለማሳደስ 5 ሚሊዮን ብር ወጭ ተደርጓል፡፡ የፕሪሚዬር ሊግ ስታንዳርድ እንዲኖረው አፈር የነበረው ሜዳ ሳር ለብሷል፡፡ መቀመጫ አልነበረውም፤ ተሰርቶለታል። ሻወር ቤት፤ ሽንት ቤት… ሁሉም አስፈላጊ ነገሮች ተሰርተውለታል፡፡
በኮሜንታተርነት የምታገኘው ክፍያ አለህ? የምሰራው ለእግር ኳስ ፍቅር ብዬ ነው፡፡ ምንም የምጠይቀው ክፍያ የለም፡፡ ያው ጨዋታውን የማስተላልፈው በስልክ እንደመሆኑ፣ በአንድ ጨዋታ እስከ 200 ብር ካርድ እሞላለሁ፡፡ ስፖንሰሮቼ ግለሰቦች ናቸው፡፡ ስልኬ ላይ እየደወሉ “ጨዋታ ለምታስተላልፍበት ካርድ እንሞላለን” ብለው ይረዱኛል፡፡ የስታዲየም መግቢያ የሚከፍሉልኝም እነዚህ ስፖርት አፍቃሪዎች ናቸው፡፡
በቋሚነት ስፖንሰር ከሚያደርጉህ ኩባንያዎች ጋር ለምን አትሰራም?
የምሰራው ለማትረፍ ብዬ አይደለም፡፡ የእኔ ዋና ትኩረት ስፖርት አፍቃሪው ቤተሰብ የሚደግፈውን ክለብ ውጤት በትኩሱ ማግኘት አለበት የሚል ነው። በአርባምንጭ ከህፃን እስከ አዛውንት ስታዲየማም ገብቶ ክለቡን ሲደግፍ ማየት ያስደስተኛል፡፡ ወደፊት አርባምንጭ በሚገኘው ኤፍኤም ሬድዮ ለማስተላለፍ የክለቡ ቦርድ እየጣረ እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ ያን ጊዜ ከቋሚ ስፖንሰር ኩባንያዎች ጋር እንሰራለን ብዬ አስባለሁ፡፡
የደቡብ ክልል እግር ኳስ ጥሩ እድገት እያሳየ ነው። አሁን ፕሪሚዬር ሊግ የገቡ ክለቦች ብዛት አራት ደርሷል። በሌላ በኩል ከአርባምንጭ የሚወጡ ተጫዋቾች በውጤታማነታቸው እየታወቁ መጥተዋል። የደቡብ ክልል እግር ኳስ የስኬት ምስጢር ምን ይመስልሃል?
አርባምንጭ በየሰፈሩ ሜዳ ነው፡፡ ከ5 ዓመትህ ጀምሮ ኳስ ትጫወታለህ፡፡ በ1970ዎቹ የታዳጊ ቡድን ውድድሮች ነበሩ፡፡ የስፖርት መምህራኖች ናቸው የታዳጊ ውድድሮችን የጀመሩት፡፡ አሁን ሃይሌ ደጋጋ በሚባል ትምህርት ቤት ሰለሞን ውሹ የሚባል የስፖርት መምህር ነበር፡፡ እኔን ሁሉ አሰልጥኖኛል፡፡ ይህ አይነቱ የታዳጊዎች ውድድር አሁን ብዙ የለም። ይህ መመለስ አለበት፡፡ አርባ ምንጭ ካፈራቻቸው ታዋቂ ተጨዋቾች መካከል ከድሮው ተስፋዬ ፈጠነ ይጠቀሳል፡፡ ከአሁኑ የብሄራዊ ቡድን አባላት ደግሞ ደጉ ደበበና አበባው ቡጣቆ ከዚያው የወጡ ናቸው፡፡ ደጉ እና አበባው የሲቃላ ልጆች ናቸው፡፡ ከልጅነታቸው ጀምሮ አውቃቸዋለሁ፡፡ ስፖርት ይወዳሉ፣ በጠዋት ተነስተው በልዩ ስሜት እና ፍቅር ሲሰሩ አያቸው ነበር። አርባምንጭ ምግቡም ልጆቹን የሚያጠነክር፡፡ የዚያ ከተማ ልጆች በአሳ ፤ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በስጋ ያደጉ ናቸው፡፡ አሳ አዘውትረው መብላታቸው በሳል አድርጓቸዋል፡፡ ስጋው፤ አትክልቱ እና ፍራፍሬው ደግሞ ጠንካራ ተክለሰውነት አዳብሮላቸዋል፡፡ በአርባምንጭ በየዓመቱ በወረዳዎች መካከል ብዙ ስፖርቶችን የሚያካትት ውድድሮች ይደረጋሉ። በሁለት እና ሶስት ዓመት ለፕሪሚዬር ሊግ ክለቦች እና ለብሄራዊ ቡድን የሚበቁ ምርጥ ተጨዋቾች መውጣታቸው አይቀርም፡፡ የደደቢት እግር ኳስ ክለብ በከተማው የታዳጊ ፕሮጀክት እየሰራ መሆኑ በአርባምንጭ ያለውን አቅም ያሳያል፡፡ የፕሪሚዬር ሊጉ ተሳታፊ ክለቦች ከደቡብ ክልል ጨምረዋል፡፡ ሃዋሳ ከነማ አለ፤ ሲዳማ ቡና፤ አርባምንጭ እና አሁን ደግሞ ወላይታ ዲቻ፡፡ በብቃታቸው አነፃፅር ብትለኝ… ጠንካራው እና ልምድ ያለው ሃዋሳ ቀዳሚ ነው፡፡ ከዚያ አርባምንጭ እና ሲዳማ ቡና፤ ቀጥሎ ገና በፕሪሚዬር ሊጉ ብቃቱ የሚፈተነው ወላይታ ዲቻ ብዬ በደረጃ አስቀምጣቸዋለሁ፡፡
ለወደፊቱ ምን አቅደሃል?
ምን መሰለህ ፍላጎቴ? የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጨዋታን በቀጥታ በማስተላለፍ ብቃቴን ማሳየት ነው። መነሻዬን ክለብ አድርጌያለሁ፡፡ ወደፊት ግን የብሄራዊ ቡድን ጨዋታዎችን ማስተላለፍ ነው የምፈልገው፡፡ ግብዣው ይኑር እንጂ ብሄራዊ ቡድን በሴካፋ እና በሌሎች ውድድሮች ሲጫወት ባስተላልፍ ምኞቴ ነው፡፡ አሁን ያለው ብሄራዊ ቡድን ባለው ፍቅር እና አንድነት በጣም ነው የምኮራበት፡፡ ካለፈው ሁለት ዓመት ወዲህ ብሄራዊ ቡድኑ በፍፁም ታታሪነት እና ጀግንነት ያስመዘገበው ውጤት፣ በጣም የምደነቅበት እና የምኩራራበት ነው፡፡ አሁንም ጳጉሜ አራት ከሴንትራል አፍሪካ ሪፐብሊክ ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን 3ለ1 አሸንፎ፣ ለቀጣዩ ውድድር እንደሚበቃ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ሁለቱን ጎሎች ጌታነህ ከበደ፣ አንዱን ሽመልስ በቀለ ያገባሉ ብዬ እገምታለሁ፡፡

ኢ.ኤል ጄምስ ትባላለች፡፡ ፎርብስ መጽሔት ባወጣው የደራሲዎች አመታዊ ሽያጭ ዝርዝር አንደኛ ሆናለች - “50 ሼድስ ኦፍ ግሬይ” በተሰኘ መፅሃፏ፡፡ ከዚ መፅሃፍዋ ያገኘችው የገንዘብ መጠን 95 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ መጽሐፉ በሦስት ተከታታይ ክፍል (Trilogy) የሚተረክ ሲሆን በስምንት ወር ውስጥ ሰባ ሚሊዮን ኮፒ ተሸጧል፡፡ መጽሐፏን ወደ ፊልም ለመቀየር በሲኒማ ሰሪዎች ተጠይቃ በመስማማቷ ተጨማሪ አምስት ሚሊዮን ብር ትርፏ ላይ ታክሎላታል፡፡ በ2014 ፊልሙ ሲኒማ ቤቶችን ያናውጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ከዚህች ሴት ደራሲ (ኢ.ኤል ጄምስ) ድንገተኛ ስኬት በፊት ከፍተኛ ሻጭ የነበረው ጄምስ ፓተርሰን ነበር፡፡ ዘንድሮ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል፡፡ ሴቷ ደራሲ በአራት ሚሊዮን ብር በልጣ አስከትላዋለች፡፡ ለአራት ተከታታይ አመታት የያዘውን ደረጃም ነጥቃዋለች፡፡ ጄምስ ፓተርሰንን “አሌክስ ክሮስ” እና “ማክሲመም ራይድ” በተሰኙ ድርሰቶቹ ድፍን አለም ያውቀዋል፡፡ በአመት አምስት መጽሐፍት ጽፎ (አምርቶ) ለማሳተም በመብቃቱ ይጠቀሳል፡፡ እሱን በመከተል ሶስተኛ ደረጃ ላይ ያለችው ሱዛን ኮሊንስ ናት፡፡ 55 ሚሊዮን ዶላር ትርፍ ከመጽሐፏ ሽያጭ አግኝታለች፡፡ መጽሐፏ “ዘ ሀንገር ጌምስ” ይሰኛል፡፡ ወደ ፊልምም ተቀይሯል፡፡ በዚሁ አመት የ”ሀንገር ጌምስ” ተከታይ የሆነው ፊልም “ዘ ሀንገር ጌምስ ካቺንግ ፋየር” የሲኒማን አለም እንደሚነቀንቅ ይጠበቃል፡፡

ታላቁ የፖፕ ሙዚቃ ንጉስ ማይክል ጃክሰን ከሞተ አራት አመት ሆነው፡፡ የሟቹ ቤተሰብ ግን አሁንም የሞቱ ምክያኒያት አልተዋጠልኝምና ይመርመርልኝ ማለቱን ቀጥሏል፡፡ ምርመራው በአንደኛነት ያነጣጠረው የሙዚቃ ንጉሱን የልብ ጤና ይከታተል በነበረው ዶክተር ኮንራድ ሙሬ ላይ ነው፡፡ የክሱ አይነት፡- በስህተት ነብስ ማጥፋት (involuntary manslaughter) እና የታማሚውን የጤና ሁኔታ ያላገናዘበ ንዝህላልነት የሚል ነው፡፡ በዚህ ፍርድ ሂደት ላይ የማይክል ጃከሰን የቀድሞ ሚስት (ዴቢ ሮው) በእንባ እየታጠበች ስለ ሟቹ ባሏ ባህሪ ተናዝዛለች፡፡ ትዝታዋን በመመርኮዝ የሰጠችው ምስክርነት የዚህ ሳምንት ትኩስ ዜና ሆኖ ሰንብቷል፡፡

በየዓመቱ በነሐሴ ወር የሚዘጋጀው የሸራተን የስዕል አውደ ርዕይ ሊቀርብ ነው፡፡ “Art of Ethiopia 2013” በሚል ርዕስ የሚቀርበው አውደ ርዕይ፤ በኢትዮጵያ ያሉ የጥበቡ ፈርጀ ብዙ ገፅታዎችን የሚያሳዩ 500 ያህል ሥዕሎች ይቀርቡበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከነዚህ ስራዎች ከመቶ አስር እጅ በቅርፃ ቅርፅ ላይ ያተኩራል የተባለለት ትልቅ አውደ ርዕይ፤ በሚቀጥለው ዓርብ ነሐሴ 24 ቀን 2005 ዓ.ም ተከፍቶ እስከ ነሐሴ 27 በየእለቱ ከቀኑ 4 ሰዓት እስከ ምሽቱ 4 ሰዓት ለህዝብ ክፍት ሆኖ ይቆያል፡፡ በዝግጅቱ 450 ሰዓሊዎች ስራዎቻቸውን እንዲታይላቸው አቅርበው “የምርጦቹ ምርጥ” ለአውደርዕዩ መቅረቡንና ከነዚህም ሩቡ እጅ የሴት ሰዓሊያን ስራ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሸራተን አዲስ ላለፉት አምስት ዓመታት በየዓመቱ ታላቅ የስዕል አውደርእይ እያሳየ ይገኛል፡፡ አውደርእዩ በአዲስ አበባ የሚገኙ የስዕል ትምህርት ቤቶችን ለማጠናከር ያለመ ነው፡፡

Page 4 of 17