በአዲስ አድማስ “እንጨዋወት” አምዱ የሚታወቀው ደራሲና ወግ ፀሃፊ ኤፍሬም እንዳለ ያዘጋጀው “የዓለም ታላላቅ ታሪኮች ለሕጻናት” መፅሃፍ ለንባብ በቃ፡፡ መፅሃፉ የሮቢን ሁድ፣ ሮቢንሰን ክሩሶ፣ “ሪፕ ቫን ዊንክል እና ሌሎች ታላላቅ ሰዎችን ታሪኮች ይዟል፡፡ 86 ገፆች ያሉት የሕጻናት መጽሐፍ፤ በጃፋር መጻሕፍት መደብር በ20 ብር እየተሸጠ ነው፡፡ ኤፍሬም እንዳለ በቅርቡ ያሳተመውን የስኬት መፅሃፍ ጨምሮ የተለያዩ የወግና የትርጉም ሥራዎችን ለንባብ ማቅረቡ ይታወቃል፡፡

“… እኔና ባለቤቴ የልጅ ያለህ ስንል ነበር ብዙ ጊዜ ቆይተናል፡፡ ተስፋ ቆርጠን በተቀመጥንበት ጋብቻ በፈጸምን በሰባት አመት እርግዝና መጣ፡፡ በጣም ተደሰትን፡፡ ሕክምናውንም በወጉ በሰአቱ ጀመርን፡፡ ባለቤቴ ዘጠኝ ወር ሙሉ ሕክምናዋን ስትከታተል እኔም አብሬያት እየሄድኩ ስለነበር የምርመራውን ውጤት ተከታትያለሁ፡፡ እርግዝናው ልክ ዘጠኝ ወር ከአንድ ሳምንት ሲሆነው ግን ችግር ተፈጠረ፡፡ በድንገት ታማለችና ወደቤት ድረስ ተባልኩኝ፡፡ እኔም በፍጥነት ከቤት ደርሼ ወደ ሆስፒታል ወሰድኩዋት። እንደደረስን የጽንሱ የልብ ምት ቆሞአል የሚል መልስ ነበር ከሐኪሙ የተነገረን፡፡ ምክንያቱስ? አልኩኝ፡፡ እኛም ምክንያቱን ለጊዜው አናውቅም...የሚል ነበር መልሳቸው። ባለቤቴ ሙሉ ምርመራ አደረገች፡፡ ምንም የጤና ችግር አልታየባትም፡፡ ነገር ግን ሊወለድ ሲጠበቅ ልጃችን በድንገት ሳይወለድ ጠፋ፡፡ ደግሞም ወንድ ነበር ፡፡ እኔም ባለቤቴም በጣም ነው ያዘንነው፡፡ በእርግጥ ሰዎች የሚያያድገውን ይስጣችሁ እያሉ ይመርቁናል፡፡ እኛ ግን በድጋሚ እርግዝናው እንዳይከሰት ፈራን …”
ቴዎድሮስ መልካሙ/ከለቡ/
ተሳታፊያችን እንዳቀረቡት ሀሳብ አንዳንድ ቤተሰቦች በተለያየ ምክንያት በእርግዝና ላይ ያለ ልጃቸውን ገና ሳይወለድ ያጣሉ፡፡ ሕጻናት ገና ሳይወለዱ የሚሞቱበት (still birth) ምክንያት ምንድነው? ስንል ጥያቄ ያቀረብን ሲሆን ለዚህ ጥያቄ ማብራሪያ የሰጡን ዶ/ር ብርሀኑ ሰንደቅ የጽንስና ማኅጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ናቸው፡፡ ዶ/ር ብርሀኑ ሰንደቅ በአሁኑ ወቅት በመስራት ላይ የሚገኙት በማሪ ስቶፕስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ነው፡፡
ጥ/ ያልተወለዱ ልጆች (still birth) ህይወት የሚያጡበት ምክንያት ምንድን ነው ?
መ/ still birth እድሜው በየሀገራቱ የተለያየ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ከ28/ሳምንት በላይ ያሉት ሳይወለዱ እንደሞቱ የሚቆጠር ሲሆን ከዚያ በታች ግን ጽንሱ እንደተቋረጠ እንጂ እንደሞት አይቆጠርም፡፡ ነገር ግን አንዳንድ አገሮች እስከ ሀያ ሳምንት አንዳንዶች እስከ አስራ ስድስት ሳምንት ዝቅ ይላሉ፡፡ የአለም የጤና ድርጅት የሚገልጸው ግን ከሀያ ስምንት ሳምንት ጀምሮ እና በክብደትም ከ500/አምስት መቶ ግራም በላይ ሆነው የጠፉትን still birth ይላቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ከሀያ ስምንት ሳምንት በላይ እና በኪሎዋቸውም ከአንድ ኪሎ በላይ ከሆኑ እንደ still birth ወይንም ጠፍተው እንደተወለዱ ይቆጠራል፡፡
ጥ/ still birth ወይንም ጠፍተው የሚወለዱ ልጆች ምን ያህል ያጋጥማል?
መ/ በአለም አቀፍ ደረጃ ከ3.2/ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ልጆች ጠፍተው ይወለዳሉ፡፡ በእርግጥ በኢትዮጵያ እንደዚህ ጥርት ብሎ የሚታወቅ የጥናት ውጤት ባይኖርም በታዳጊ አገሮች ግን በአምስት እጥፍ ከአደጉት ይበልጥ ችግሩ ይከሰታል፡፡ የዚህ ልዩነት ምክንያት ደግሞ የክኖሎጂው እድገት ያለመኖር፣ የክሮሞዞም ጥናት ማካሄድ አለመቻል፣ አልትራሳውንድ ቀኝም ግራም አለመኖር፣ የእርግዝን ክትትል በአግባቡ አለመኖር፣ በምጥ ሰአት በፍጥነት ወደ ህክምና ተቋም አለመምጣት፣ ጽንሱ በሆድ ውስጥ እንዲጠፋ ምክንያት ከሚሆኑት መካከል ናቸው፡፡ ስለዚህም በታዳጊ አገሮች ያለው የልጆች ሳይወለዱ መጥፋት ችግር ከአደጉት ጋር ሲነጻጸር በአምስት እጥፍ የሚበልጥ ሲሆን በኢትዮጵያም ቀላል ችግር እንዳልሆነ ይመታል፡፡ ጠፍተው የሚወለዱ ልጆች ከምጥ በፊት እና በምጥ ሰአት የሚሞቱት ሲሆኑ ነገር ግን ከተወለዱ በሁዋላ የሚሞቱት የጨቅላዎች ሞት ከሚባለው የሚካተት ነው፡፡
ጥ/ still birth ወይንም ጠፍቶ ለመወለድ ምክንያቶቹ ምንድናቸው?
መ/ ከ25-45 % ድረስ ያለው ምክንያት ከጽንሱ ጋር የተያያዘ ነው፡፡
ጽንስ ከሀያ ስምንት ሳምንት በሁዋላ ሳይወለድ እንዲጠፋ ምክንያት ከሚሆኑት መካከል የክሮሞዞም ችግር አንዱ ነው፡፡ ይህ ችግር ያለባቸው ከማህጸን ወጥተውም መኖር የማይችሉበት ሁኔታ ይታያል፡፡
ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ የክሮሞዞም ችግር ሳይኖርባቸውም አካላዊ ጉድለት ሊኖር ይችላል፡፡ የህብለሰረሰር ክፍት መሆን ፣ጭንቅላትን ውሀ መሙላት፣ ጭንቅላት አለመሰራት የመሳሰሉት ጉድለቶች ካሉ ሚወለዱም መኖር አይችሉም፡፡
እንደቂጥኝ በመሳሰሉ በሽታዎች ምክንያት ኢንፌክሽን ሊከሰት ስለሚችል ልጆች ሳይወለዱ ሊጠፉ ከሚችሉባቸው ምክንያቶች መካከል ነው፡፡
ሌላው ከእንግዴ ልጅ እና እትብት ጋር በተያያዘ ሊከሰት የሚችል ችግር ሲሆን በእርግጥ ከእናትየው ወይንም ከጽንሱ ጋር በተያያዘ የሚከሰት ሊሆን ይችላል፡፡
የእንግዴ ልጅ ከተፈጠረበት ቦታ ያለጊዜው መላቀቅ እንደችግር ከሚቆጠሩ መካከል ነው፡፡ ይህም እናትየው የደም ግፊት ካለባት፣ በሆዳቸው ላይ የተለያየ አደጋ መውደቅ...የመኪና አደጋ..ድብደባ ...ወዘተ ከተከሰተ ጽንሱ ከእናትየው ሊያገኘው የሚችለው ምግብ እና አየር በሙሉ ስለሚቋረጥ ሊጠፋ ይችላል፡፡
የጽንስ መቀጨጭ በሚከሰትበት ጊዜም የእንግዴ ልጁ የሚሰራቸው አገልግሎቶች ማለትም ከእናት ወደልጅ ምግብ፣ ኦክሲጅንና ሌሎችም ፍላጎቶች በደንብ እንዳይተላለፉ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡
እትብት አንገት ወይንም እግር ላይ በሚጠመጠምት ጊዜ የጽንሱ ሕይወት ሊቋረጥ ይችላል፡፡
ከእናትየው ጋር በተያያዘ፡-
በእድሜ ዘግይቶ ማርገዝ ወይም ከልክ በላይ የሆነ ውፍረት ፣የደም ግፊት እና ስኩዋር በሽታ ልጆች ጠፍተው እንዲወለዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ እድሜ በጨመረ ቁጥር የደም ግፊት እና ስኩዋር በሽታ እንዲሁም የክሮሞዞም ችግር ሊከሰት ይችላል፡፡ ከልክ በላይ የሆነ ውፍረትም እንደዚሁ የደም ግፊት እና ስኩዋር በሽታ ሊያስከትል ይችላል፡፡
ምንም ምክንያት የሌላቸው፡-
ጠፍተው ከሚወለዱ ልጆች 1/4 እሩብ ያክሉ በዚህ ምክንያት ሊባል የሚችል ምክንያት የሌላቸው ናቸው። እነዚህ ከጽንሱ ወይንም ከእንግዴ ልጁና ከእትብቱ አሊያም ከእናትየው ጋር በተያያዘ የሚጠቀስ ችግር ሳይኖር ምክንያታቸው ሳይታወቅ የሚጠፉ ናቸው፡፡ በእርግጥ ይህ ችግር በአደጉትና እንደእኛ ባሉ ሀገሮች ሲታይ ልዩነት ይኖረ ዋል፡፡ እሩብ ያህል ጠፍተው የሚወለዱ ልጆች ምክንያታቸው አይታወቅም ሲባል በአደጉ ሀገራት የምርመራው ክኖሎጂ በተሟላበት የሚታወቅ ሲሆን እንደእኛ በአሉ ሀገራት ግን በግልጽ ምክንያቱ ይህ ነው ብሎ ለመለየት አስቸጋሪ ሊሆን ስለሚችል ምናልባትም እስከ 60% ያህሉ ምክንያታቸው ያልታወቀ ተብለው ሊመዘገቡ ይችላሉ፡፡
ጥ/ ጽንሱን ያረገዘችው እናት የአኑዋኑዋር ሁኔታ እንደችግር የሚታይበት አጋጣሚ ይኖር ይሆን?
መ/ እርግጥ ከላይ የተዘረዘሩት ምክንያቶች ጎልተው የሚታዩ በመሆናቸው እንጂ እነሱ ብቻ ናቸው ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌም ጽንሱ ሊቀጭጭ ከሚችልባቸው ምክንያቶች አንዱ እናትየው የእጽ ተጠቃሚ መሆን ወይንም ሲጋራ ማጤስ የመሳሰሉት ሲሆን ይህም የምግብ ፍላጎትን የሚቀንስ ነው ፡፡ አደንዛዥ እጾች በደም ዝውውር ላይም የሚያመጡት ተጽእኖ አለ፡፡ በዚህም ምክንያት የእንግዴ ልጁ ከእናትየው ወደልጁ የሚያስተላልፈውን ማንኛውንም ጠቃሚ ነገር እንዳይፈጽም አጋጣሚውን ስለሚፈጥር ጽንሱ እንዲቀጭጭና ህይወቱን እንዲያጣ የሚያስችልበት አጋጣሚ በርካታ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ግን በስራ አጋጣሚ ሊያጋጥም የሚችል ጎጂ የሆነ የኬሚካል ሽታ ወይንም ለመዝናናት ለማማር ሲባል የሚደረግ ኬሚካል የሆነ ምርት በጽንስ ላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል፡፡ እርግዝና ደሕንነት የተሞላበትን አካባቢ ይሻል፡፡ ልጅ ሙሉ የሰውነት አካሉን የሚመሰርተው እስከ ሁለት ወር ወይንም ስምንት ሳምንት ድረስ ነው፡፡ በዚያ ጊዜ ውስጥ የሚከሰት ማንኛውም ችግር በልጁ ላይ የአካል ጉድለትን የሚያደርስ ይሆናል፡፡ አንዲት ሴት ለማርገዝ ስታቅድ በቅድሚያ የህክምና ባለሙያ ጋ በመሄድ ውስጣዊም ሆነ ውጫዊ አካሌ ለእርግዝና የሚያበቃኝ ነውን? በስራዬ ወይንም በመኖሪያዬ አካባቢ ማድረግ የሚገባኝ ጥንቃቄ ምንድነው? በተለያዩ የጤና ሁኔታዎች የምትወስደው መድሀኒት ካላት በጽንሱ ላይ ችግር ያስከትላል? አያስከትልም? ለመፍትሔው ምን ማድረግ ይጠበቅብኛል? በማለት ማማከር ይጠበቅባታል፡፡
ጥ/ ቤተሰብ ጠፍቶ የተወለደ ልጅ ሲገጥመው ቀጣዩ እርምጃ ምን መሆን ይገባዋል?
መ/ ልጅ ጠፍቶ ሊወለድ የቻለበትን ምክንያት ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ በእርግጥ ሁልጊዜም ይገጥማል የሚባል ባይሆንም ለጊዜው ግን በየትኛው ምክንያት ሳይወለድ ሊጠፋ እንደቻለ ማወቅ ለሕሊናም እረፍት ይሰጣል፡፡ ቤተሰብ ፈቃደኛ ከሆነም ልጁ ገና ከማህጸን እንደወጣ ከራስ ጸጉር እስከ እግር ጥፍሮቹ እንዲሁም የአካል ጉድለት መኖር ያለመኖሩን እና ምክንያቱ ምን እንደሆነ ለማወቅ ጥንቃቄ የተሞላው ምርመራ ይደረ ግለታል፡፡ የእትብቱ ክብደት ፣የእንግዴ ልጁ ክብደት ፣እትብቱ በቂ የደም ስሮች እንዳሉት እና እንደሌሉት የመሳሰሉትን ሁሉ ማየት ይገባል፡፡ የክሮሞዞም ችግር አለ ወይንስ የለም ? የሚለውንም በምርመራው ወቅት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ምክንያቱን ማወቅ አስፈላጊ የሚሆንበት ምክንያት ምናልባት ቤተሰቦች ሊያስተካክሉት የሚችሉት ነገር ካለ እርምጃ መውሰድ እንዲችሉ ለማድረግ ጭምር ነው፡፡

Published in ላንተና ላንቺ
Saturday, 10 August 2013 11:42

ሸዋ ሃይፐርማርኬት

ፈር ቀዳጁ የገበያ ማዕከል

የውጭ ገንዘብ መመንዘሪያ (ፎረክስ ቢሮ)
በየሳምንቱ ሰርፕራይዝ አለ
የንፅህና መስጫ (ላውንደሪ)
ብዙ መሸመት ያሸልማል
የሕፃናት ማቆያ

 ዴፓርትመንት ስቶር፡- የተለያዩ ምርቶችና ሸቀጦች በዓይነት ዓይነታቸው ተለይተውና የራሳቸው ስፍራ ተሰጥቷቸው ለሸማቾች የሚቀርቡበት በጣም ትልቅ የችርቻሮ ገበያ ማዕከል ነው፡፡ የገበያ ማዕከሉ እስከ መቶ ዴፓርትመንት ሊኖረው ይችላል፡፡ ለምሳሌ፣ ራሱን የቻለ የልብስ፣ የምግብ፣ የእርሻ፣ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች፣ የቤት ዕቃዎች፣ ዴፓርትመንት (ክፍል) ሊኖረው ይችላል። 

ሱፐርማርኬት፡- ተገልጋዩ ራሱ የሚፈልገውን ዕቃ በመምረጥ (ለምሳሌ የምግብ፣ የቤት ዕቃ፣ የሕፃናት መገልገያ፣ …) የሚገዛበት የችርቻሮ ገበያ ማዕከል ነው፡፡
ሃይፐርማርኬት፡- ዴፓርትመንት ስቶርንና ሱፐርማርኬትን አጠቃሎ የያዘ በጣም ግዙፍ (ሱፐር ስቶር) የገበያ ማዕከል ማለት ነው፡፡
* * *
በአገራችን ዴፓርትመንት ስቶር ለመኖሩ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ሱፐርማርኬት ግን ሸዋ ሱፐር ማርኬት “ሱማሌ ተራ” ከተከፈተበት ከ1958 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት 50 ዓመታት ያህል ይታወቃል፡፡ ሸዋ ሱፐርማርኬት፣ አምስት የገበያ ማዕከላትን በቦሌ፣ በጦር ኃይሎች፣ በሳር ቤት፣ በሲኤምሲ አካባቢ ከፍቶ ሲሠራ ከቆየ በኋላ፣ ሰሞኑን ደግሞ መገናኛ አካባቢ ከቤተልሔም ፕላዛ ፊት ለፊት በዘፍመሽ ግራንድ ሞል (ትልቅ የገበያ ማዕከል) ስድስተኛ ቅርንጫፉን ከፍቷል - “ሸዋ ሃይፐርማርኬት” በሚል፡፡ የሸዋ ሱፐርማርኬት መስራችና ባለቤት ማን እንደሆኑና ከምን ተነስተው እንደከፈቱት ወደ ኋላ ላይ እመለስበታለሁ፡፡
በ3ሺ ካ.ሜ ላይ ባረፈው ሸዋ ሃይፐርማርኬት ሲገቡ፣ መገረምዎና መደነቅዎ አይቀርም፡፡
የዕቃዎች ዓይነት፣ ብዛትና ጥራት አጃኢብ ያሰኛል፡፡ በገበያ ማዕከሉ ፈልገው የሚያጡት ነገር የለም፡፡ “ደንበኞቻችን የሚፈልጉትንና መርካቶም ሆነ ሌላ ቦታ ሄደው የሚገዙትን ማንኛውንም ነገር (ምግብ፣ የቤት ዕቃ፣ የሕፃናት መገልገያ …) እዚሁ በአንድ ቦታ እንዲያገኙ አድርገናል” ይላሉ የሸዋ ሃይፐርማርኬት ሥራ አስኪያጅ አቶ ግርማይ ዓለማየሁ፡፡
አሁን በምሥራቅ በር እንግባና እንጐብኝ። የነገው አገር ተረካቢ ሕፃናት ጤናማ ሆነው፣ ምቾትና ፍላጐታቸው ተጠብቆ እንዲያድጉ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡ ከተወለዱበት ዕለት ጀምሮ የሚያስፈልጋቸው ነገር በዘርፍ በዘርፉ ተዘጋጅቷል። ምግብ፣ የገላ ማጠቢያ፣ መታቀፊያ፣ ልብስ፣ ጡጦ፣ ቅባቶች፣ ሻምፑዎች፣ የንፅህና መጠበቂያ ዳይፐር፣ የገላ መጥረጊያ ዋይፐር፣ ከፍ ሲሉ ደግሞ እንደ የዕድሜያቸው ጫማና ነጠላ ጫማ፣ የተለያዩ መጫወቻዎች፣ አሻንጉሊቶች፣ መኪኖች፣ የተለያየ መጠን ያላቸው አልጋዎች፣ የመመገቢያ ጠረጴዛ፣ ዳዴ ከማለታቸው በፊት የሚጠቀሙበት ጋሪ፣ ግራውንድ ፕላስ ዋን መጫወቻ ቤት፣ … ኧረ ስንቱ! ተዘርዝሮ አያልቅም፡፡ “አራት መደርደሪያ ሙሉ፣ (ከፊትና ከጀርባ ስምንት) ሸቀጦች መዘጋጀታቸው ለሕፃናት የተሰጠውን ትኩረት ያመለክታል” ብለዋል ሥራ አስኪያጁ፡፡
ከሕፃናት መደብር ቀጥሎ የጽሕፈት መሳሪያዎች ናቸው ያሉት፡፡ ከትንሿ ነገር እስከ ትልቁ የፋይል ማቀፊያ 300 ዓይነት የጽሕፈት መሳሪያዎች አሉ፡፡ በዳር በኩል በስተግራ ኮስሞቲክስና ሽቶ፣ ጥራት ያላቸው ሞባይሎችና መለዋወጫዎች፣ ልዩ ልዩ የወርቅና የብር ጌጣጌጦች ይታያሉ፡፡ ሸሚዞች፣ የአዲዳስ ጫማዎች፣ ቱታዎችና የስፖርት ትጥቆች፣ … የሚሸጡበት ቡቲክ እየተዘጋጀ ነው፡፡ ከዚያ ፊት ለፊት ደግሞ የተለያየ ዓይነትና መጠን ያላቸው የጉዞ ሻንጣዎች (ላጌጅስ)፣ በፀሐይ ኃይል (ሶላር ሲስተም) የሚሠሩ የኤሌክትሪክ ዕቃዎች፣ አምፑሎችና ኮምፒዩተር አክሰሰሪዎች (ሃርድ ዌርና ሶፍት ዌር) … በወግ በወጉ ተሰትረዋል፡፡
ከቡቲክ ቀጥሎ የዲኤስቲቪ ዕቃዎች፣ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች፣ የተለያዩ መጠን ያላቸው ቴሌቪዥኖች፣ ምድጃዎች፣ ፍሪጆች፣ ማይክሮዌቭ፣ የልብስ ማጠቢያ ማሽን፣ ውሃ ማሞቂያ፣ ጁስ መጭመቂያ፣ ፔርሙሶች፣ ሽንኩርት መፍጫ፣ … ከፊትና ከጀርባ 10 መደርደሪያ ሞልተዋል፡፡ ከዚያ በታች ያሉት የተለያዩ የአገር ውስጥና የውጭ የንፅህና መስጫ ዱቄትና ፈሳሽ ሳሙናዎች (ዲትሬጀንቶች) ናቸው፡፡
ስንዴና ጤፍም ሃይፐር ማርኬት ገብተዋል። ነጭ ጤፍ፣ ማኛ፣ ሠርገኛ፣ ቀይ ጤፍና የስንዴ ዱቄት በ50 ኪሎ እየሆኑ ተሰናድተዋል፡፡ ሌላው የሚገርመው “ትንሿን መርካቶ” የሚመስለው የጥራጥሬና የቅመማ ቅመም ገበያ ነው፡፡ የአገር ውስጥና የውጭ ለውዝ፣ ተልባ፣ የተለያየ ዓይነት ቦሎቄ፣ ፈንዲሻ፣ ማኛ (ማሽ) ምስር፣ ሽንብራ ዱቤ፣ ባቄላ፣ ቡና፣ ምስርና አተር ክክ፣ የቅንጬ እህሎች፣ የተፈጨ ጐመን ዘር፣ አብሽ፣ ዘለላ ሚጥሚጣ፣ ከሙን፣ ኮረሪማ፣ ሄል፣ ቀረፋ … ኧረ ተዘርዝሮ አያልቅም፡፡ ብቻ 70 ዓይነት ጥራጥሬና ቅመማ ቅመም ንፅህናቸው ተጠብቆ በመስተዋት ቤት ተቀምጠው፣ በዲጂታል ሚዛን እየተመዘኑ ይሸጣሉ፡፡
በአዲስ አበባ ታዋቂ የሆኑት የሙልሙል ዳቦ ሠራተኞች፣ እዚያው በገበያ ማዕከሉ የድርጅቱን መሳሪያ በመጠቀም ትኩስ ዳቦና ኬክ በመጋገር ለደንበኞች ያቀርባሉ፡፡ ክሬም ኬክ ግን ሌላ ቦታ ተጋግሮ ይቀርባል፡፡ ሃይፐርማርኬቱን ልዩ የሚያደርገው ጣፋጭ የሶሪያ ኬኮችን እዚያው ጋግሮ ማቅረቡ ነው፡፡ ባቅላባና ኩኪስን ጨምሮ 22 ዓይነት ጣፋጭ ምግቦች ያሰናዳል፡፡ ከዚያው ጐን ደግሞ ትኩስ ፒዛና በርገር ይጋገራል፡፡ በደንበኛው ፍላጐት መሠረት፣ የዶሮ፣ የበሬ፣ የበግ፣ የአትክልት፣ … 26 ዓይነት በርገሮችና ፒዛ ማግኘት ይችላል፡፡ ዓሳም አለ፡፡ ደንበኛው ከፈለገ በቋንጣ፣ ካልፈለገ ትኩሱን “ፊሌቶ አውጡልኝ” ብሎ መውሰድ ይችላል፡፡ የወተት ተዋጽኦዎችም በርካታ ናቸው። የሚያስጐመጅ የሥጋ ዓይነትም አለ፡፡ እንደ ደንበኛው ፍላጐት፣ ንቅል፣ የክትፎ፣ የወጥ፣ የጭቅና፣ የበርገር፣ … ማግኘት ይቻላል፡፡
ዝቅ ሲሉ፣ ፒያሳ አትክልት ተራ የገቡ ይመስልዎታል፡፡ ፒያሳ የሚገኘው አትክልትና ፍራፍሬ በሙሉ፣ በንፅህና ታሽጐ ቀርቧል፡፡ በኪሎ በኪሎ ተመዝነው ተፈጥሮዊ መልክና ጣዕማቸውን ይዘው እንዲቆዩ ፍሪጅ ውስጥና መደርደሪያ ላይ ተለይተው ተቀምጠዋል፡፡
ሃይፐርማኬቱን ልዩ የሚያደርገው ሌላው ነገር ዘመናዊ የሕፃናት ማቆያው ነው፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውን ይዘው ዕቃ ፍለጋ የገበያ ማዕከሉን ሲዞሩ፣ ልጆች ሊደክማቸው ይችላል፡፡ ስለዚህ፣ ሞግዚቷ ልጆቹን ተቀብላ፣ መጫወቻ ወደተሟሉለት ማቆያ በመውሰድ እንደየዕድሜያቸው ታዝናናቸዋለች። “ወላጅ ልጆቹን ይዞ ከሠራተኛው ጋር ሊመጣ ይችላል፡፡ ያኔ ልጆቹ እየተጫወቱና እየተዝናኑ እንዲቆዩም ይደረጋል” ብለዋል ሥራ አስኪያጁ፡፡ በማቆያው ሲጫወት ያገኘነው ዳኒ ቦጃ 7 ዓመቱ ነው። የ11 ዓመቷ እህቱ ሳሮኒያም አብራው ነበረች፡፡ ልጆቹ ማቆያውን በጣም ወደውታል። “ለልጆች በጣም ጥሩ መጫወቻ ስለሆነ በጣም ደስ ይላል” ብላለች - ሳሮኒያ፡፡ እቃ ለመግዛት ከወንድ ጓደኛዋ ጋር መጥታ በሃይፐርማርኬቱ ውስጥ ያገኘናት ራሔል ግርማም ስለ ገበያ ማዕከሉ ጠይቄአት፤ “በጣም ደስ ብሎኛል፤ ከጠበቅነው በላይ ነው ያገኘነው፡፡ የምንፈልገው ዕቃ በሙሉ አለ። ከእንግዲህ ወዲያ ዕቃ መግዛት ስንፈልግ ወደዚህ እንመጣለን” ብላለች፡፡ ራሔል ዋጋውም ተመጣጣኝ መሆኑን ተናግራለች፡፡ “ስለ ዋጋው ጉዳይ ከእሱ ጋር (የወንድ ጓደኛዋን ማለቷ ነው) እየተወያየን ነበር፡፡ በሌላ ሱፐርማርኬቶች የምናውቃቸው ዕቃዎች በዚያው ዋጋ እዚህ አሉ፡፡ ስለዚህ ጥሩ ዕድል ነው፤ ብዙ ሳንለፋ ሁሉንም እዚሁ እንገበያለን ማለት ነው፡፡ በጣም ደስ ብሎኛል” በማለት አስተያየቷን ገልጻለች፡፡
እዚያው ያገኘነው ሌላው አስተያየት ሰጪ ማንደፍሮ “የአገራችንም ሆኑ የውጭ እንግዶች ይህን የገበያ ማዕከል በማግኘታቸው በጣም ደስ ብሎኛል። ለአገራችንም ክብር ነው” ብሏል፡፡
የገበያ ማዕከሉ ባንክ ቤት አለው፣ በቅርቡ ደግሞ የንፅህና መስጫው ላውንደሪ ሥራ እንደሚጀምር አቶ ግርማይ ተናግረዋል፡፡ “ሌላው ለየት የሚያደርገን ባንካችን ሸዋ ፎሬክስ ቢሮ ነው፡፡ አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና እንደመሆኗ መጠን፣ የውጭ እንግዶችና ቱሪስቶች ይመጣሉ፡፡ እነዚህ የውጭ አገር ደንበኞቻችን ወደዚህ ሲመጡ ዕቃ መግዛት ይፈልጋሉ፤ ነገር ግን ምንዛሪ በማጣት ይቸገራሉ። መመንዘሪያ ባንክ ፍለጋ እንዳይንከራተቱ ከንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ጋር በመተባበር ሸዋ ፎሬክስ ቢሮ ከፍተናል፡፡
“ይህን ቢሮ የከፈትነው እኛ የውጭ ምንዛሪ (ዶላር) መቀበል ስለማንችል ነው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ደንበኞች ቼክ ይዘው ሊመጡ ይችላሉ፡፡ ቼኩን አንቀበልም ብለን ደንበኛውን ከምንመልስ፣ “ሸዋ ፎሬክስ” ቼኩን ተቀብሎ ገንዘብ ያለውና የሌለው መሆኑን አረጋግጦ፣ ፈርሞ ይሰጠናል፡፡ ስለዚህ ቼክ ይዘው የሚመጡ ደንበኞችም ይስተናገዳሉ ማለት ነው፡፡ ሌላው አዲስ ነገር ላውንደሪያችን ነው፡፡ ደንበኛው ወደኛ ሲመጣ ልብሶቹ እንዲታጠብለት ይሰጣል፡፡ በቀጠሮው ወይም በሌላ ጊዜ ሲመጣ ደግሞ ልብሶቹን ይዞ ይሄዳል፡፡ ይህ ለየት ያደርገናል” በማለት አስረድተዋል፡፡
ሸዋ ሃይፐርማርኬት ለ350 ሰዎች የመኪና ማቆሚያ አዘጋጅቷል፡፡ የገበያ ማዕከሉ 220 ሠራተኞች ያሉት ሲሆን ሠራተኞቹ ደንበኛ ማለት ምንድነው? ከእኛ ምን ይፈልጋል? እንዴት ነው ማስተናገድ የሚገባን? … በሚሉ ነጥቦች ዙሪያ ስልጠና እንደተሰጣቸው አቶ ግርማይ ገልጸዋል። ከዚህም በተጨማሪ ንብረታቸውን ከሌባ ለመጠበቅና የደንበኞቻቸውን ደህንነት ለማረጋገጥ 58 ካሜራዎችና አንድ የሴኩሪቲ መከታተያ ካሜራ አለ፡፡
ለሸዋ ሃይፐርማርኬት መመሥረት መነሻ የሆኑት ሐጂ ቡሰር አህመድ ናቸው፡፡ ሐጂ ቡሰር፤ ፒያሳ፣ ወደ ሸዋ ዳቦ በሚያወጣው መንገድ በሸቀጣ ሸቀጥ ንግድ ይተዳዳሩ እንደነበር አቶ ግርማይ ይናገራሉ። ከዚያም በ1958 ዓ.ም “ሱማሌ ተራ” አካባቢ የመጀመሪያውን ሸዋ ሱፐርማርኬት ከፈቱ፡፡ ከብዙ ጊዜ ጥረትና ትግል በኋላ ሁለተኛውን ቦሌ አካባቢ “ሸዋ ሾፒንግ ሴንተር”፣ ሦስተኛውን ጦር ኃይሎች አካባቢ፣ ሳር ቤትና ሲኤምሲ አካባቢ ከፈቱ፡፡
ሐጂ ቡሰር በአሁኑ ወቅት በሕይወት የሉም፤ ከስድስት ወር በፊት በሞት ተለይተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሸዋ ሃይፐርማርኬትን የሚመራው ልጃቸው አቶ ሐሰን ቡሰር ሲሆኑ የታዘዙ ዕቃዎችን ለማስጫን ውጭ አገር ስለሄዱ ልናገኛቸው አልቻልንም፡፡
“በኢትዮጵያ የመጀመያ የሆነ በ3ሺህ ካ.ሜ ላይ ያረፈ ሃይፔርማርኬት (የተሟላ የገበያ ማዕከል) ለማዘጋጀት ከፍተኛ ጥረትና ብዙ ሚሊዮን ብሮች የጠየቀን ቢሆንም፤ የሕዝቡን ፍላጐት ለማርካት ቆርጠን ተነስተናል” ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ አሁንም ህብረተሰቡ “ይኼ ቀረ፣ ይኼ ጐደለ” ካላቸው ለማሟላት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
ዓላማችን የሕዝቡን ፍላጐት ማርካት ነው፤ ትልቅ የገበያ ማዕከል እስከሆነ ድረስ ሁሉንም ነገር ማሟላት አለበት ብለዋል፡፡ አንዳንድ ዕቃዎች ለምሳሌ የአሳማ ሥጋ፣ መጠጥና ሲጋራ የለም ተብለው የተጠየቁት ሥራ አስኪያጁ፤ “ለጊዜው እነዚህ ነገሮች የሉም። ነገር ግን በምን መልኩ መቅረብ እንዳለባቸው ጥናት እየተካሄደ ነው፡፡ ከዚያም በጥናቱ መሠረት ተፈጻሚነት ያገኛል” ብለዋል፡፡
የገበያ ማዕከሉ ባለፈው ማክሰኞ ተከፍቷል። በዕለቱ የ1,500 ብር ዕቃ ለገዙ ወይም በዕለቱ መጥተው ባይገዙም በቅርቡ ለመግዛት ላቀዱ 250 ደንበኞች የ30 በመቶ ቅናሽ ማድረጋቸውን ገልፀዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በየሳምንቱ በፍጆታ ዕቃዎች ላይ የ “ሰርፕራይዝ” ፕሮግራም መኖሩን ተናግረዋል፡፡ “ለምሳሌ ካሁን ቀደም ያደረግነው ስኳር 20 ብር በሚሸጥበት ወቅት እኛ ግማሽ በግማሽ ቀንሰን በዘጠኝ ብር ሸጠናል።
ዘይትም በጣም በተወደደበት ጊዜ እንደዚሁ አድርገናል፡፡ ሰርፕራይዝ የምናደርገውን ነገር አንገልጽም፡፡ “ለምሳሌ ካሁን ቀደም ያደረግነው ስኳር 20 ብር በሚሸጥበት ወቅት እኛ ግማሽ በግማሽ ቀንሰን በዘጠኝ ብር ሸጠናል፡፡ ዘይትም በጣም በተወደደበት ጊዜ እንደዚሁ አድርገናል። ሰርፕራይዝ የምናደርገውን ነገር አንገልጽም፡፡ ‘ዛሬ ይኼ አልፏችኋል፡፡ ለሳምንት ደግሞ?’ ብለን በጥያቄ ምልክት በመተው፣ በሳምንቱ ውስጥ ለኅብረተሰቡ በጣም አስፈላጊ ነው ያልነውን ነገር ሰርፕራይዝ እናደርጋለን” በማለት አስረድተዋል፡፡
ይህ ብቻም አይደለም፡፡ የመጀመሪያዎቹ 10 ከፍተኛ ሸማቾች የሚሸለሙበትም ፕሮግራምም አለ፡፡ “ለደንበኛው አንድ ካርድ ተዘጋጅቶለት ይዞ ይሄዳል፡፡ በየወሩ የገዛቸውን ሸቀጦች ዋጋ እዚያ ላይ ይሞላል፡፡ ያ ይደመርና በወሩ ከፍተኛ ሸማች ለሆኑ 10 ደንበኞች እንሸልማለን፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከሼባ ማይልስ ጋር ተነጋግረን የውጭ ጉዞ ሽልማት አዘጋጅተናል፡፡ ደንበኛችን በየጊዜው በሚገዛው እቃ ዋጋ መጠን ነጥብ ይያዝለትና ተጠራቅሞ ዱባይ ወይም ሌላ ቦታ መሄድ ከፈለገ እኛ ወጪውን እንሸፍንለታለን፡፡ ይኼ ደንበኛውን ለማበረታታትና ስለገዛ ብቻ የምንሸልምበት ፕሮግራም ነው፡፡
ሌላው ደግሞ በክፍያ ወቅት ደንበኞቻችን በወረፋ ብዛት እንዳይጨናነቁ 14 የኤሌክትሮኒክስ መክፈያ ቦታ አዘጋጅተናል፡፡ መክፈያዎቹ በኔትወርክ ስለተያያዙ ደንበኛው ሰው ወዳልበዛበት ሄዶ መስተናገድ ይችላል” በማለት አቶ ግርማይ ዓለማየሁ አስረድተናል፡፡በማስፋፊያው ሁለት ተመሳሳይ ሃይፐር ማርኬት ለማቋቋም ታቅዷል፡፡

ማንኛውም ጤናማ ሰው ቢያንስ በሣምንት አንድ ቀን በፍልውሃ መታጠብ ይገባዋል

እርጅና የተጫጫናቸው ክፍሎች፣ የወላለቁ የቧንቧ መክፈቻና መዝጊያዎች፣ የተላላጡ ግድግዳዎች፣ ያረጁ ፎጣዎች፣ የተንሻፈፉ ነጠላ ጫማዎች፣ እድሜ የተጫናቸው ሠራተኞችና ተራ ጠባቂ ደንበኞች በብዛት የሚገኙበት ሥፍራ ነው-ፍልውሃ፡፡ ከህመማቸው ለመፈወስና፣ የሻወር አገልግሎት ለማግኘት ከፍቅረኞቻቸው፣ ከባለቤቶቻቸውና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለመታጠብ በርካቶች ወደ ፍልውሃ ይሄዳሉ፡፡ ድርጅቱ የሃያ አራት ሰዓት አገልግሎት የሚሰጥ ቢሆንም ሥፍራው ሁልጊዜም በደንበኞች እንደተጨናነቀ ነው፡፡
በንጉሡ ዘመን ተሰርተው አገልግሎት መስጠት የጀመሩት ክፍሎች፤ እርጅና ተጫጭኗቸውና እድሣት ናፍቋቸው ዛሬም ድረስ ደንበኞቻቸውን እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡
ሥፍራው ለአዲስ አበባ ከተማ ምሥረታም ያበረከተው አስተዋፅኦ በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡ እቴጌ ጣይቱ ከእንጦጦ ቤተመንግስታቸው ተነስተው ወደእዚህ ሥፍራ ለመውረዳቸው ምክንያታቸው በአካባቢው የተፈጥሮ ፍልውሃ መገኘት ነበር፡፡ እቴጌይቱ በፍልውሃ አካባቢ ውበት ተማርከው ጊዜያዊ ማረፊያቸው ካደረጉት በኋላ፣ በሥፍራው በሚገኘው የተፈጥሮ ፍልውሃ መታጠብ የየዕለት ተግባራቸው ሆነ፡፡ አካባቢውን ወደዱት፡፡ በፍልውሃው ፍቅር ወደቁ፡፡ ይህ ደግሞ ባላቸውን (አፄ ሚኒሊክን) አሣምነው የአገሪቱን መናገሻ ከተማ እስፍራው ላይ ለመቆርቆፍ እንዲችሉ ማድረጉን የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡
ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ፍልውሃዎችን በብዛት ከታደሉት አገራት መካከል አንዷ ናት፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የምሥራቅ አፍሪካው ታላቁ ስምጥ ሸለቆ የአገሪቱን አብዛኛውን ክፍሎች አቋርጦ የሚያልፍ በመሆኑ ነው፡፡ የአዲስ አበባው ፍልውሃ፣ የሶደሬው አባድር፣ ወንዶገነት፣ ወሊሶና አምቦ ኢትዮጵያ ሆቴል የተፈጥሮ ፍልውሃ ከሚገኝባቸው የአገራችን አካባቢዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ እነዚህ የተፈጥሮ ፀጋዎችም ከቱሪዝም መስህብነታቸው እና ከገቢ ማስገኛ ምንጭነታቸው በተጨማሪ ለፈውስ አገልግሎት እየዋሉ ነው፡፡ በፍልውሃው አማካኝነት በርካቶች ከያዛቸው ደዌ እንደሚፈወሱ እንሰማለን፡፡ የጥንት አባቶቻችን ለዘመናት ያለ ሳይንሳዊ ዕውቀት ሲጠቀሙበት የኖሩት ይኸው የተፈጥሮ ፍልውሃ፤ አሁን ዘመናዊና ሣይንሣዊ በሆነ መንገድ ጥናትና ምርምር እየተደረገበት ይገኛል፡፡
የተፈጥሮ ፍልውሃን በማጥናት ሥራ ላይ ተጠምደው የሚውሉ ተመራማዎች አሁን አዲዲስ የጥናትና የምርምር ውጤቶችን ይፋ እያደረጉ ነው፡፡ በቅርቡ በአሜሪካ የሚገኙ ተመራማሪዎች ይፋ ያደረጓቸው መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ከ37°C (ከሰላሣ ሰባት ድግሪ ሴንትግሬድ) እስከ 39°C ድረስ ሙቀት ያለው የተፈጥሮ ፍልውሃ ለጤና እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ ማንኛውም ጤናማ ሰው ቢያንስ በሣምንት አንድ ቀን በዚህ የሙቀት መጠን ውስጥ ባለ የፍልውሃ መታጠብ ወይም መዘፍዘፍ ይኖርበታል፡፡ ይህም በምግብ ውስጥ በበቂ ሁኔታ ልናገኛቸው የማንችላቸውን ንጥረ ማዕድናትንና የተለያዩ ለሰውነት እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ማግኒዚየም፣ ሶዲየምና ካልሲየም የተባሉ ማዕድናትን ለማግኘት ያስችለናል፡፡ እነዚህ ማዕድናት ደግሞ ለተለያዩ በሽታዎች ፈውስ እንደሆኑ የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
የተፈጥሮ ፍልውሃዎች እንደሚገኙበት ሥፍራ በማዕድን ይዞታቸው መጠንና በአሲዳምነታቸው እንደሚለያዩ የጠቆመው ይኸው ጥናት፤ በውሃው ውስጥ የሚገኙት ማዕድናት የሚሰጡትም የፈውስ አገልግሎት እንደየሁኔታው ሊለያይ እንደሚችል አረጋግጧል፡፡
የተፈጥሮ ፍልውሃን ፈዋሽነት በሚያጠናው ባላኒዮሎጂ (Balaneyology) በተሰኘው የጥናትና ምርምር ዘርፍ የተሰማሩ የአሜሪካ ሳይንቲስቶች ባደረጉት መረጃ፤ ፍልውሃ በሁለት የተለያዩ መንገዶች ሊገኝ ይችላል፡፡ የመጀመሪያው (Filtrate hot spring) የተባለውና በመሬት ስንጥቅ አማካይነት ወደ ከርሰ ምድር ውስጥ የገባው የዝናብ ውሃ እጅግ ሞቃታማ በሆነው የመሬት ክፍል ውስጥ ደርሶ፣ በውስጡ ከሚገኙ የከርሰ ምድር ማዕድናት የያዘው ሞቃት ውሃ፣ በመሬት ውስጣዊ ግፊት አማካኝነት ወደ መሬት ገፅ በመውጣት በፍል ውሃነት ይከሰታል፡፡ ሌላው የተፈጥሮ ፍልውሃ (Primary hot spring) የተባለው ሲሆን ይህ ውሃ የሚፈጠረው በተፈጥሮ በከርሰ ምድር ውስጥ በሚደረግ እንቅስቃሴ ነው፡፡ በከርሰ ምድር ውስጥ በሚደረግ እንቅስቃሴ አማካኝነት በርካታ ማዕድናትና ንጥረ ነገሮች ከውሃው ጋር ይቀላቀላሉ፡፡ በመሬት ግፊትም ውሃው ወደ ገፀ ምድር ሲወጣ በርከት ያሉ ለጤና እጅግ ጠቃሚ የሆኑ ማዕድናትንና ንጥረ ነገሮችን ይዞ ይወጣል፡፡ በሁለቱ የተለያዩ መንገዶች የሚገኘው ፍልውሃ፤ የተለያዩ የማዕድንና የጋዝ መጠኖች ያሉት ሲሆን የሶዲየም ክሎራይድ ይዘትም አለው፡፡ ከ3-5% የሚደርስ የሶዲየም ክሎራይድ ይዘት ያለው የተፈጥሮ ፍልውሃ፤ ለመገጣጠሚያ ብግነት፣ ለቁርጥማት ለነርቭ በሽታ፣ ለአጥንት መሳሳት፣ ለጡንቻ መተሳሰር እና መሰል የጤና ችግሮች መድሃኒት መሆኑን ጥናቶች አረጋግጠዋል፡፡
የተፈጥሮ ፍልውሃ ከዚህ በተጨማሪ ለቆዳ በሽታዎች፣ ለመተንፈሻ አካላት ችግሮች እፎይታን ይሰጣል፡፡ የአዕምሮን የማሰብ ችሎታ ከፍ ለማድረግ፣ ድብርት ሲጫጫነን፣ ጤናማ የልብ ምት እንዲኖረን፣ ሰውነታችን ውስጥ የሚፈጠሩ መርዛም ንጥረ ነገሮችን ለማስወገድና የሆርሞን ስርዓታችንን ለማስተካከል የተፈጥሮ ፍልውሃዎች ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው፡፡
ከከርሰ ምድር የሚገኙት የተፈጥሮ ፍልውሃዎች በሚኖራቸው የሙቀት መጠን እንደሚለያዩ መረጃው ጠቁሞ፤ በዚሁ የሙቀት መጠናቸው ልክም በአራት የተለያዩ መደቦች እንደሚከፈሉ ገልጿል፡፡ የሙቀት መጠናቸው ከ25°C በታች የሆኑና ከከርሰ ምድር የሚገኙት ቀዝቃዛ የምንጭ ውሃ (Cold Spring water) ሲባሉ፣ የሙቀት መጠናቸው ከ25-34°C ድረስ ያሉት ደግሞ ለብ ያለ (Tepid Spoizing Spring water) ይባላሉ፡፡ ከ34-42°C ድረስ ያሉት የገፀ ምድር ውሃ ሞቃታማ (Warm Spring water) በሚል መጠሪያ ሲታወቁ ከ42°C በላይ ያሉት ደግሞ ፍልውሃ (hot Spring water) ተብለው ይጠራሉ፡፡
ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርነው እነዚህ የተለያየ የሙቀት መጠን ያላቸው የተፈጥሮ ፍልውሃዎች፤ እንደሙቀት መጠናቸውና እንደማዕድን ይዘታቸው የሚሰጡት የፈውስ አገልግሎትም ይለያያል፡፡ የሙቀት መጠናቸው ከፍ ያለ ፍልውሃዎች እንፋሎታቸው ከባድ በመሆኑ የደም ግፊት፣ የልብ ድካም፣ የካንሰር፣ የጉበትና የኩላሊት ህሙማንና ነፍሰጡር ሴቶች ባይጠቀሙ ተመራጭ እንደሆነ የጤና ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡

Published in ዋናው ጤና
Saturday, 10 August 2013 11:23

ተናጋሪዋ ምድር

የትግራይ ጉዞ ማስታወሻ
‹‹ኧረ ጉድ በዛ ኧረ ጉድ በዛ፤
በጀልባ ተሻግሮ አበሳን ቢገዛ”
ዛሬ የጥበብ ጉዟችን ይጠናቀቃል፤ግን ገና የምናያቸው ድንቅና ታሪካዊ ቦታዎች አሉ። ወደ አክሱም ስንጓዝ ጊዜው በመምሸቱ ምክንያት በይደር ያለፍናት አንድ ገናና ታሪክ የተፈፀመባት ቦታ አለች፡- አድዋ! እንኳንስ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ጥቁር አፍሪካዊ ሁሉ “አድዋ” የሚለው ስም ሲነሳ መንፈሱን የሚነሽጠው አንዳች መግነጢሳዊ ኃይል አለ፡፡ እሱም በ1888 በዕብሪተኞቹ ጣሊያኖች ላይ የደረሰው ዘግናኝ ውድቀት ነው፡፡
አድዋ የአካባቢው ስም ይሁን እንጂ ኢትዮጵያውያንን ከጣሊያን መንጋ ታድገው ዛሬም ከእነ ግርማ ሞገሳቸው የቆሙ ተራሮች ብዙ ናቸው። አቀማመጣቸው በራሱ ዕውቅ ባለሙያ ለውበት ተጨንቆ የቀረፃቸው ይመስላሉ፡፡ አንዳንዶችን ለመጥቀስ ያህል የሰሎዳ ተራራ ቀዳሚው ነው። ቀዳሚ የሚሆንበት ምክንያትም አፄ ምኒሊክ ሰፍረውበት ስለነበር ነው፡፡

“ጊዮርጊስ ጓጓ” ከተባለው ቦታም ንጉሰ ነገስቱ አስቀድሰዋል፡፡
ጳውሎስ ኞኞ “አጤ ምኒሊክ” በተባለው መፅሀፉ ላይ በወቅቱ የነበረውን አሰላለፍ ሲገልፅ “ራስ መኮንን የሀረርጌን ጦር ይዘው አድዋ ከተማን፣ራስ ሚካኤል የወሎን ጦር ይዘው ሰሎዳ ተራራን፣ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት የጎጃምን የጦር እየመሩ ከጦርነቱ ፊትለፊት የሚገኘውን እንደ አባገሪማን፣ ራስ መንገሻ ዮሐንስ ዓዲአቡንን ሲቆጣጠሩ አጤ ምኒልክ፣ እቴጌ ጣይቱ፣ ራስ ወሌና ዋግሹም ጓንጉል ሰራዊታቸውን ይዘው የኋላ ደጀን ሆኑ” (ገፅ204) ይላል፡፡ ተክለፃድቅ መኩሪያ ደግሞ እያንዳንዱ የጦር አበጋዝ በስሩ ያሰለፈውን ሰራዊት ከመዘርዘር ውጪ የተሰለፉበትን ቦታ አይገልጡም፡፡
ያም ሆነ ይህ አድዋ ላይ በጣሊያን በኩል 7560 ጣሊያኖች፣ 7100ጥቁር ወታደሮች ያለቁ ሲሆን ከኢትዮጵያ ወገን 7000 ሞተው 10‚000 መቁሰላቸውን ጳውሎስ ጽፎአል (ገፅ 211)፡፡ ቁጥሩን በተመለከተ ከተለያዩ ጸሐፊዎች የሚጠቀሰው አኃዝም የተለያየ ነው፡፡
ለማንኛውም ሰሎዳ፣ እንዳአባ ገሪማ፣ የገሰሰው ተራራ፣ ኪዳነ ምህረት፣ ሰማያታ (ትልቁ ተራራ ነው)፣ “ፎልስ ኪዳነምህረት” ፣ማርያም ሸዊቶ ወዘተ ተራሮች ዛሬም በኩራት ተኮፍሰው ሲታዩ ጠላታቸውን ድባቅ መትቸው ለሀገራቸው ዘብ የቆሙ ጀግኖች ይመስላሉ፡፡ ዛሬም “ሃገሬን አትንኩ!” የሚል የአደራ ቃል የሚያስተላልፉ ባለ ሕያው ታሪክ ግዙፍ የታሪክ ቦታዎች ናቸው፡፡
በነገራችን ላይ “ፎልስ ኪዳነ ምህረት” የተባለው ጣሊያኖቹ ኪዳነ ምህረት የተባለውን ስትራቴጂክ ቦታ ያዝን ብለው ሌላ ተራራ በመያዛቸው የተሰጠ ስያሜ መሆኑን አቶ ከበደ አማረ ነግረውናል፡፡ የአድዋን ተራሮች የጎበኘናቸው እንደ ሌላው ዝም ብለን አይደለም፡፡ የጀግንነት ግጥሞች በተጓዦች ተነብበዋል፤ቀረርቶም ሰምተናል፤ ግን የገደልነውም ሆነ የማረክነው ጣሊያን አልነበረም፡፡ ምን አልባት የአድዋ ተራሮች “እንዲህ አርጎም ጀግና የለ?” ብለው ታዝበውን ይሆን?
ሆኖም አንበሶቹ ራስ መኮንን ፣ንጉሥ ተክለሃይማኖት፣ራስ መንገሻ ዮሐንስ፣ ራስ ሚካኤል፣ ወዘተ ከንጉሰ ነገስታቸው ፊት ዘገራቸውን እየነቀነቁ፣ ጎራዴያቸውን እየሰበቁ ከእሳተ ነበልባል በሚያቃጥል ወኔ ሲፎክሩ፣ግዳያቸውን ሲያስመዝግቡ ደረቱ በትዕቢት ተወጥሮ ኢትዮጵያን ቅኝ ግዛቱ ሊያደርግ የመጣ የጣሊያን ጀኔራል በወጥመድ የተያዘች አይጥ መስሎ በፍርሃት ሲንቀጠቀጥ ታየኝና “ምነው በዚያ ዘመን ኖሬ የዚያ ቅዱስ ታሪክ ተሳታፊ በሆንኩ?” ብዬ አሰብሁ፡፡ “ኧረ ጉዱ በዛ፣ ኧረ ጉዱ በዛ፣
በጀልባ ተሻግሮ አበሻን ሊገዛ” ብለው ያቅራሩትን ጀግኖች በዓይነ ህሊናዬ እያስዋልሁ፡፡ አድዋ ላይ ያየነው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃም ሌላው አስደሳች ጉዳይ ነው፤ ግራ ካሱ፣ አብርሃ ወአጽብሃ እና ገረዐልታ ተራሮች ላይ ያየነው የደን ጥበቃና እንክብካቤ አድዋ ተራሮች ላይም ተገቢ ትኩረት ተሰጥቶት፣ ውበት ዳግም እየተፈጠረች መሆኗን ተገንዝበናል፡፡
አድዋ ላይ ባለቁት ወገኖቻችን እያዘንን፤ ደግሞ ባስገኙት ዓለምአቀፍ የጥቁሮች ድል እየተኩራራን በቅርብ ርቀት የምትገኘውን ጥንታዊት ከተማ የሃን ለመጐብኘት ተንቀሳቀስን፡፡ የሃ በ800 ዓመተ ዓለም የተገነባ ቤተመቅደስ ዛሬም በእማኝነት ቆሞ የሚገኝባት ታሪካዊት ከተማ ናት፡፡ ቤተ መቅደሱ የተገነባው ከድንጋይ ብቻ ነው፤ ገንቢዎቹ ጭቃም ሆነ ሲሚንቶ ለማጣበቂያነት አልተጠቀሙም፡፡ የስነ ምድር እና የስነ ህንፃ ተመራማሪዎች በጥናት እንዳረጋገጡት፤ ህንፃው ያረፈው ከአለት ላይ ነው። የገነቡትም ሴማውያን ሲሆኑ ፀሐይ እና ጨረቃን ያመልኩ ነበር፡፡
ቤተመቅደሱ 12 ምሰሶዎች፣ አምስት ክፍሎች፣ ያሉት ባለ ፎቅ ህንጻ እንደነበር አስጐብኝያችን አስረድተውናል፡፡ ቦታው በወቅቱ የአገሪቱ ዋና ከተማ የነበረ ከመሆኑም በላይ 150 ነገሥታት ኖረውበታል፡፡ የመንግሥቱ ሥርወ መንግሥት መጠሪያም “ዳአመት” በመባል ይታወቃል፡፡ ቤተመቅደሱ ከ12-15 ሜትር ከፍታ እንዳለው ከአስጐብኟችን የተረዳን ሲሆን ድንጋይ በድንጋይ ላይ ብቻ በመደራረብ በ800 ዓመተ ዓለም የተሰራ ህንጻ ለ2900 ዓመታት ያለምንም ጥገና መቆየቱ የዚያኔዎቹን ወገኖቻችንን ጥበብ በእጅጉ ተደናቂ ያደርገዋል፡፡ አገራችን “የ3000 ዓመት የሥርዓተ መንግሥት ታሪክ አላት” ሲባል ተረት አለመሆኑንም በእርግጠኝነት ያስረዳል። ለመሆኑ ለህንፃው የተጠቀሙባቸው ድንጋዮችን እንደእንጨት የጠረቡበት መሣሪያ ምን ነበር ይሆን? መቸም ትግራይን የጐበኘ አዕምሮ ሁሉ በተለያዩ ጥያቄዎች መወጠሩ ግድ ነው፡፡
እስከ ሶስት ሜትር የሚረዝሙ ድንጋዮች የተደረደሩበት ህንፃ ለዚያን ያህል ረጅም ዘመን የመቆየቱ ምስጢር በጀርመን ባለሙያዎቹ እየተጠና ከመሆኑም ሌላ ቅርሱ እንዳይጠፋ ጥገና ሊደረግለት ዝግጅት መጀመሩን በጉብኝታችን ወቅት ተመልክተናል፡፡
ቤተመቅዱ ዓድአካውህ ላይ ያየነው አልሙጋህ የተባለው ጣኦትም ይመለክበት ነበር ተብለናል፤ መሥዋዕቱ ይቀርብበት የነበረው፤ ወይም የመሰዊያው ቦታ (ክፍል)፣ የመስዋዕቱ ደም የሚወርድበት ከድንጋይ የተጠረበ ቱቦ በእጅጉ የሚያስደንቁ ናቸው፡፡ ግድግዳው ብቻ ሳይሆን ወለሉ ራሱ በሰፋፊ ጥርብ ድንጋዮች የተስተካከለ ሲሆን ዛሬም ውበቱ አልደበዘዘም፡፡
ከቤተመቅደሱ ምስራቃዊ አቅጣጫ የቆመው የአቡነ አፍጼ ቤተክርስቲያንም ሌላው ግዙፍ ሃብት ነው፡፡ አቡነ አፍጼ በ6ኛው መቶ ክፍለዘመን ከሮምና ከመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ወደ አገራችን ከመጡ ዘጠኝ ቅዱሳን አንዱ ናቸው፡፡ ቤተክርስቲያኑ የተገነባው በጥንታዊ ህንፃ ላይ መሆኑን፣ እንዲያውም ከየሃ ቤተመቅደስ ላይ ልዩ ልዩ ጌጣጌጦችን ወስደው ቤተክርስቲያኑን እንዳስጌጡበት በጉብኝታችን ተገንዝበናል፡፡ በገዳሙ ወስጥ እጅግ ጥንታዊ የሆኑና ከቤተመቅደሱና ከአካባቢው የህንፃ ፍርስራሾች የተገኙ በሳባ፣ በግዕዝና በግሪክ ቋንቋዎች የተፃፉባቸው ድንጋዮች፣ የብራና መጻሕፍት፣ መስቀሎችና ልዩ ልዩ ንዋየቅድሳት ይገኛሉ፤ ግን አቀማመጣቸው አንዱ በሌላው ላይ የተደራረበ ስለሆነ ለልዩ ልዩ ጉዳቶች ሊዳርጓቸው ይችላልና ቢታሰብበት መልካም ነው፡፡
ከአቡነ አፍጼ ቤተክርስቲያን ምስራቃዊ አቅጣጫ በቅርብ ርቀት ላይም ሌላ አስደናቂ ነገር ተገኝቷል። ስፋቱ 24 በ24 የሆነ ሰፊ ቤተመንግሥት፡፡ ስሙ “ግራት በዓል ገብሪ” የሚባል ሲሆን ከየሃ ምኩራብ በፊት አገልግሎት ይሰጥ እንደነበር ከአስጐብኛችን ተረድተናል፡፡ ምንም እንኳ በጀርመንና በሃገራችን ባለሙያዎች እየተጠና ቢሆንም ህንጻው ከ5-6 ፎቆች እንደነበሩት ተረጋግጧል፡፡
በተከታታይ ጽሑፎቼ ለመጠቆም እንደ ሞከርኩት ሃገራችንን እንኖርባታለን እንጂ አናውቃትም፤ እናማርራታለን እንጂ አንመረምራትም፤ ከፈረንጆች ማረጋገጫ ካላገኘን ስለ እኛ የምናየውን አናምንም፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ዘመናዊ ትምህርት በአገራችን ሲጀመር በፈረንጅ ሥርዓትና በፈረንጅ አስተማሪ መቀረጹ ይመስለኛል፡፡
ከዚህ ሌላ ስለ ቱሪዝም ያለን አመለካከት በእጅጉ ደካማ ነው፤ እስራኤላውያን ኢየሱስን ሰቅለው ሌላ ኢየሱስን (መሲሕ) ይጠብቃሉ፡፡ ግን ገቢያቸዉን ለማሳደግ ሲሉ ኢየሱስ የሄደበትን፣ የተቀመጠበትን፣ የተገረፈ፣ የተገፈፈበትን፣ የተሰቀለበትንና የተነሳበትን ቦታ ሁሉ በሥርዓት ያስጐበኛሉ፡፡ በዚህም የትየለሌ ዶላር ዓመት ሙሉ ይዝቃሉ፡፡ ግብጾችም ሙሴን በቅርጫት አድርገው እንደ ቆሻሻ ዓባይ ወንዝ ውስጥ እንዳልጣሉት ሁሉ ዛሬ ካይሮ በርባራ ቤተክርስቲያን ግቢ ውስጥ በሚገኝ ቦታ የአይሁድ ቤተ መቅደስ ገንብተው “ሙሴ የተጣለው በዚህ ቅርጫት ነበር” እያሉ ያስጐበኛሉ፡፡ ፎቶግራፍ ማንሳት እየከለከሉም በጉቦ የፖሊሶቻቸውን ኪስ ያደልባሉ፡፡ እኛ ግን ዛሬም እንደተኛን ነን፡፡ ምንአልባት የትግራይ ክልላዊ መንግሥት እንደ ተፈጥሮ ጥበቃው በዚህም ፋና ወጊ ተግባር አከናውኖ ማየት ይናፍቀኛል፡፡ ሌላውና ከአገራችን ይልቅ ባዕድ ናፋቂ እንድንሆን ያደረገን ምክንያት የነገሥታቱ ከንቱ አስተሳሰብ ይመስለኛል፡፡ ይህም ድምሩን ህዝብ በማታለል “ከመለኮት ዘር አለን” ለማለትና ራሳቸውን ከኢትዮጵያ ህዝብ የተለየ፤ በዘራቸው ለመግዛት ብቻ የፈጣሪ ፈቃድ የታደላቸው አድርገው ለማጭበርበር ሲሉ “ሞዐ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ” የሚል ቅጽል ከስማቸው በፊት ያስቀድማሉ እንጂ “ዘእምነገደ አክሱም” አይሉም፡፡ በዚህም ኢትዮጵያዊ አንበሣነታቸው እንደሚያሳፍራቸው መረዳት ይቻላል፡፡
የአክሱም ዘራቸውን ሳይጠቅሱ ከሰሎሞን ቤተመንግሥት ውስጥ ራሳቸውን እንዴት እንደሚያገኙ ግን ለኔ እንቆቅልሽ ነው፡፡ መሪዎች የተጸየፉትን አገር ህዝቡ ቢጠላው ታዲያ ምኑ ያስገርማል? ከሰሎሞን መወለድ ማለት ዲቃላነትን መቀበል ነው፤ ዲቃሎች ያልሆኑት የላሊበላ ነገሥታትና የቅርብ ጊዜው ዳግማዊ ቴዎድሮስ በግልባጩ “ዲቃሎች” ተብለው ሲወገዙ መኖራቸው ራሱ ታሪካችንን ክፉኛ በክሎታል ባይ ነኝ፡፡
ታሪክን መበከል ባይሆን ኖሮ ነገሥታት “ከሰለሞን ዘር መጣን ከማለት ይልቅ “ከታላቋ አክሱም የተገኘን” ቢሉ ምንኛ ያኮራቸው ነበር! ለማንኛውም አገራችንን በደንብ እንዳናውቃት ካደረጉን ሰበቦች አንዱ የእነሱው የዘር ቅልውጥ ይመስለኛል፡፡
ወደተነሳሁበት ነጥቤ ልመለስና ጉዟችንን እያጠናቀቅቅ ነው፤ ግን በጉብኝታችን ወቅት ራትና ምሳ እየጋበዙ የላቀ የክብር እንግድነት አቀባበል ያደረጉልን የመላዋ ትግራይ ከተሞች፣ የክልሉ መንግሥት፣ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ፣ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ እና የኢትዮጵያ የዘላቂ ቱሪዝም ልማት ጽ/ቤት በእጅጉ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡
ደሴ ገብተናል፤ ጉዟችን የተቋጨው የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር ደሴ ቅርንጫፍ ከወሎ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባዘጋጀው ደማቅ የሥነ-ጽሑፍ ምሽትና የራት ግብዣ ነው፡፡
በዚህም የቅርንጫፍ ማኅበሩ መሪዎችንና ወሎ ዩኒቨርስቲን አድንቀናል፡፡ በአጠቃላይ የመልስ ጉዞአችን እንደ መጀመሪያው ደማቅ አልነበረም፤ በእያንዳንዱ ተጓዥ ፊት ላይ ቅሬታና የመከፋት ስሜት ይነበብ ነበር፡፡ እንደኔ ከሆነ ለዚህ ምክንያቱ “ያንን የመሰለ ታላቅ ስልጣኔ ምን በላው? እኛስ ምንድን ነን? ወደየትስ እያመራን ነው?” የሚል ሊሆን ይችላል፡፡ እንደ አንድ ቤተሰብ በፍቅር ቆይቶ መለያየቱም ሌላ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡
ለማንኛውም ያን የመሰለ ድንቅ የጥበብ ጉዞ ያዘጋጀው የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበርና ወጭውን የሸፈነው የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የምስጋናውን ብኩርና መውሰድ ይገባቸዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ሰላም!

 

Published in ህብረተሰብ
Saturday, 10 August 2013 11:17

ትውልድ የ" ማዛመድ "ዕዳው!

በዘመናዊነት አስተሳሰብ “ማዛመድ” ያለ ውዴታ የተጣለብን ፍዳ መሆኑን ቅንጣት አልጠራጠርም። ማዛመድ ማግባባት ብቻ አይደለም፡፡ ማዳቀልም ነው፡፡ የሚዳቀሉት ነገሮች ተቃራኒ መሆናቸው ግልፅ ቢሆንም፤ ተቃራኒነታቸው ተመጣጣኝ ካልሆነ ድቅያው ይቆረቁዛል እንጂ አያድግም፡፡
ለምሳሌ፤ ሴት እና ወንድ በፆታ ተቃራኒ ናቸው። ግን ተመጣጣኝ ተቃራኒዎች በመሆናቸው ይዛመዳሉ፡፡ ይፈላለጋሉ፡፡ ይፋቀራሉ፡፡ ይዋለዳሉ። ከሁለቱ ልዩነት ውስጥ አዲስ ፍሬ ይፀነሳል፡፡ ያመጣጠናቸው ተፈጥሮአቸው ነው፤ ፅንሱ ሲያድግ አዲስ ትውልድ ተብሎ ይጠራል፡፡
የሴቴ እና ወንዴውን ፆታ በሌላ ነገር መወከል እንችላለን፡፡ ለምሳሌ ፆታዎቹን በአስተሳሰብ ልንወክላቸው እንችላለን፡፡ አንደኛው ኢትዮጵያዊ አስተሳሰብ (ፆታውን ከፈለግን ወንድ ብለን እንጥራው) … ሌላኛው የምዕራባዊያንን አስተሳሰብ ሊወክልልን ይችላል፡፡ ይችላል ብቻ ሳይሆን ነውም፡፡ ፆታውን ሴት ብንለው ተቃራኒነቱን አያዳክመውም፡፡ …
በጣሊያን ፋሽስታዊ ወረራ ከደረሰብን ሽንፈት አንስቶ አሁን እስካለንበት ዘመን ድረስ ለማዳቀል የምንሞክረው እነዚህን … የሐሳብ፣ የባህል፣ የአመለካከት፣ የእምነት…ፆታዎችን ቅራኔ ነው፡፡ ከሽንፈታችን በፊትማ አለም ወደኛም እኛም ወደ አለም ሄደን መቀላቀልን አንሻም ነበር፡፡ የተሳካልን ግን አይመስለኝም፡፡ የሚዳቀሉት ማንኛቸውም ተቃራኒዎች ተመጣጣኝ ካልሆኑ የተሳካ ትውልድ ወይንም የትውልድ ማንነት አይፈጠርም፡፡
… ቴክኖሎጂን የተቀበለ እንጂ ያልፈለሰፈ አገራዊ አስተሳሰብ ቴክኖሎጂዉን ለማይመጣጠን አገልግሎት ሲጠቀምበት ቢገኝ… ተጠያቂው ትውልዱ አይደለም፡፡ ትውልዱ የራሱን አስተሳሰብ በራሱ ቋንቋ መግለፅ እየቻለ፣ በፈረንጅ ቋንቋ የአማርኛን ቅኔ ለመግለፅ ከሞከረ … ድቅያው ፍሬአማ የሚሆን አይመስለኝም፡፡
… ማዛመድ እና ማዳቀል ግን ለሰው ልጅ የተፈጥሮ ባህርይው ነው፡፡ አበሻም ሆነ ፈረንጅ የሰው ልጆች ናቸው፡፡ (እነ ፍራንስ ቦዋዝ እንደሚሉን ከሆነ!) መቅዳት እና ማስቀዳት ግዴታው በመሆኑ ያስፈልገዋል፡፡ ስለሚያስፈልገውም ደግሞ ለመቅዳት ይገደዳል፡፡ መቅዳት እና ከራሱም እንዲቀዳለት መፈለጉን በሚፈጥራቸው መልከ ብዙ ገለፃዎች ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ የዘመኑ ትውልድ የዚህ አይነተኛ ምሳሌ ነው፡፡
የቀዳው ነገር ከምንጩ ውጭ ሲሆን ነው ችግሩ። ለምሳሌ … የብሎን መንጃ (Screw driver) ከባህር ማዶ ወደ አበሻ ማንነቱ አስገብቶ ሲቀዳ … ብሎን መንጃውን “ጠመንጃ” መፍቻ ብሎ ነበር ለራሱ ትርጉም ሲል የሰየመው፡፡ ስያሜ እና ቋንቋ ስለ ነገርየው ያለንን እውቀት እና አስተሳሰብ በአጭሩ ጨምቀን የምናስቀምጥበት (abstract) ማዛመጃችን ነው፡፡ … ብሎን የሚባል ነገር በሌለበት ሀገር ላይ ከብዙ ብሎኖች እና ሜካኒካል የአሰራር ቅንብር የተሰራ አንድ እቃ መግባቱን ሳይሆን ነገርየውን “ለጠብ” አላማ ብቻ በመዋሉ የሚፈለግ መሆኑን ቃሉ ገላጭ ነው፡፡ ቃሉ “ጠብ መንጃ” ነው። ብሎን ማጥበቂያውን ወይንም ማላያውን እቃ ሊያውቀው የሚችለው ከዚህ የጠብ ፍላጐቱ ጋር አያይዞ ነው። ምንም ነገር አጥብቆም ሆነ አላልቶ አያውቅም። ባለማወቁ ጠብ መንጃን መፍቻ ብሎ ጠራው። “መፍቻ” ማለቱ ራሱ ትርጉሙ ወዲህ ነው፡፡ ከመስራት፣ ማፍረስ … ከመግጠም መንቀል እንደሚቀርበው የሚያሳይ ነው፡፡
ስለ ኮምፒውተር ያለው እውቀትም “ከጠመንጃ መፍቻው” የተለየ አይደለም፡፡ ኮምፒውተሩን ይፈልገዋል፡፡ ፊደሎቹን በብራና የጥንታዊ ጥበቡን ተጠቅሞ መጠረዝ አይችልም፡፡ መፅሐፍት ለማተም “የጉተምበርግን” ፈጠራ ይፈልገዋል። ስለሚያስፈልገው፡፡ ከባህር ማዶ ያስመጣዋል፡፡ ካስመጣው ስልጣኔ ጋር የራሱን ጥንታዊነት ደባልቆ አዲስ ድቅያ ለማፍራት ይሞክራል፡፡ … “ጥንቸል ዘላ ዘላ ከመሬት” እንደሚባለው እድሜ ልኩን ሲያዳቅል ኖሮ በስተመጨረሻ … ጥንታዊ አባቶቹ ወደ ቆረቆሩት ገዳም ገብቶ ይመንናል፡፡
ከአለም ጋር ለመዛመድ የሚያደርገው ሙከራ ራስ ምታት ሆኖበት እያለም ሌላ ሀገራዊ ግጭቶችም ልዩነቱን ያበዙበታል … በራሱ እና በሀገሩ ላይ ያሉ ብሔሮች መሀልም ያለው ተቃርኖ የመዛመድ ፍላጐት ይቀሰቅስበታል፡፡ … ግን ተቃራኒዎቹ ተመጣጣኝ ካልሆኑ መደባለቅ አይኖርም። ተመጣጣኝነት ማለት አንዱ የበለጠ፣ ሌላው ያነሰ ባለመሆናቸው እርስ በራስ እንዲቀላቀሉ፣ እንዲዛመዱ የሚያደርጋቸው ስበት ነው፡፡ ካልሆነ መደባለቅ አይቻልም፡፡ ቢደባለቁም አይዛመዱም። ያልተዛመደ ግን የተዛመደ የሚመስል ማንነቱ…በቋንቋ፣ ባህል፣ እምነት…እየተሳከረበት በመግባባት ስም ሳይግባባ እንቆቅልሽ ሆኖ ይቀጥላል፡፡
… የደራሲ ስብሐት ገ/እግዚአብሔር ዜና እረፍት ሲሰማ (በአለማየሁ ገላጋይ) ገፋፊነት የፃፍኳት አንድ ግራ የተጋባች መጣጥፍ ነበረችኝ፡፡ መጣጥፏ አሁን ከሌሎች መጣጥፎች ጋር ተዛምዳ “መልክዐ ስብሐት” የተሰኘች መፅሐፍ ሆና ተጠርዛለች፡፡
በመጣጥፏ ለመቀላቀል ወይንም ለማዛመድ የሞከርኩት ደራሲ ስብሐት ገ/እግዚአብሔርን ከአሜሪካዊው ደራሲ ኧ.ሄሚንግዌይ ጋር ነበር። መጣጥፏ ግራ የተጋባች የሆነችው ዝምድናው የተሳካ ባለመሆኑ ነው፡፡ እኔ የሞከርኩትን ሙከራ በኔ ትውልድ ስም የሚጠራ ወጣት በሙሉ የሚሞክረው ይመስለኛል፡፡ በተለያየ ዘርፍ እና አቅጣጫ ሙከራው ይከናወናል፡፡ … ሁሉም የትውልዱ አባል ለመሆን የሚፍጨረጨርለት፣ የሚሰደድለት አንድ የባህር ማዶ ማንነት አለ፡፡ ለማዛመድ ይጥራል፡፡ እኔ በደራሲ ረገድ ስብሐትን ከሄሚንግዌይ ጋር ለማዛመድ ሞከርኩ፡፡ በደንብ ካልተዛመዱ ሁለቱም ተቃራኒዎች ለየብቻቸው መኖር ቢቀጥሉ ይሻላል፡፡ ምክንያቱም ከድቅያው አዲስ እና ከሁለቱ ተቃራኒዎች የበለጠ የጠነከረ ውህድ (synthesis) አይገኝምና ነው፡፡ ካልተገኘ ደካማው ከውህዱ ውስጥ ይሞታል፡፡ ከድህነት እና ከብልጽግና የትኛው ነው ጠንካራ?
ስለዚህ የማቀላቀል ሙከራዬን እምገፋበት ይመስለኛል፡፡ ማዛመዱ በድርሰት ዘርፍ ብቻ ሳይሆን … በሙዚቃ፣ በቲያትር፣ በፍልስፍና፣ በፊልም፣ በሳይንስ … በሐይማኖት … ወዘተ እያለ የሚቀጥል ነው፡፡ ማዛመድ የቻልኩ እንደሆነ፤ የሁለቱ ተቃራኒዎች ዝምድና … ተመጣጣኝ እና አንዱ ሌላውን የመሸከም አቅም ያለው ሆነው እናገኛለን፡፡
እስቲ ሙከራዬ ላይ ትንሽ ቅርፅ ልጨምርበት። ቅርፅ ይዘትን የመሸከም አቅም አለው፡፡ ሀሳቡ እስካለ ድረስ የሚገለፅበት ቁልጭ ያለ መንገድ መገኘቱ አይቀርም፡፡ እኔ ዛሬ መግለፅ የሞከርኩት “ዝምድና” የተባለውን እሳቤ ነው፡፡ በዘርፋችን እና በዘርፋቸው፡፡ በእኛ እና በአለም መሀል፡፡ የዚህን ሀሳብ ለመግለፅ ትምህርት ቤት ስንማር ፈተና እንፈተንባት የነበረችውን የጥያቄ ቅርፅ ለመጠቀም ወሰንኩ፡፡
አዛምድ (ለሙዚቃ)
h ሀ. ጃኖ ባንድ (ሊድ ጊታር) a. ውልፍጋንግ
አማዴዮስ ሞዛርት
b ለ. አለማየሁ እሸቴ b. ጄምስ ብራውን
e ሐ. ቴዲ አፍሮ c. አሊ ፋርካ ቱሬ
f ሠ. ማሕሙድ አህመድ d. ፍራንክ ሲናትራ
g ቀ. አስቴር አወቀ e. ሮበርት ኔስታ
ማርሊ
a በ. ፕ/ር አሸናፊ
(እረኛው ባለ ዋሽንት) f. ሁሊዮ ኢግሌስየስ
d ተ. ጥላሁን ገሠሠ g. ሻዴ
c ቸ. አሊ ቢራ h. እስቲቭ ሬይቫን
ማዛመዱ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ውልፍጋንግ አማዲየስ ሞዛርትን ከፕሮፌሰር አሸናፊ ጋር በማዛመዴ የስህተት ምልክት (X) የሚሰጠኝ ካለ … ስህተቱ ከእኔ የመነጨ አይደለም፡፡
ስህተቱ ከእኔ ያልሆነው፡- የተሳሳትኩት የቱ ጋር እንደሆነ ባለማወቄ አይደለም፡፡ ላውቅ የምችለው ከብዙ መቶ አመታት የስልጣኔ ጉዞ በኋላ መሆኑ ላይ ነው፡፡
ማዛመድ ሲያቅተኝ … የራሴን ታላቅነት እፈክርና ወደ አባቶቻችን እምነት እና ትውፊት ስለማፈግፈግ እሰብካለሁ፡፡ … የፈረንጆቹን ስልጣኔ በኮምፒውተር ላይ እጭንና አደምጣለሁ፡፡
አዛምድ (ፍልስፍና)
----ሀ. ? a. ፍሬድሪክ ኒቼ
----ለ. ? b. ቶማስ አኳይነስ
----ሐ. ? c. ኢማኑኤል ካንት
----መ. ? d. ሐሮደርጋር
-b-ሠ. ዘርዐ-ያዕቆብ e. ፕሌቶ
----ረ. ? f. አሪስቶትል
----ቀ. ? g. ቅዱስ አጉስጢኖስ
“ሀ-ለ-ሐ-መ”ን ከ “A,B,C,D” ጋር ለማዛመድ ከመሞከር … “ጠብ መንጃን” ፍቅር እንዲነዳ መፀለይ ሳያዋጣ አይቀርም፡፡ “ጥንቸል ዘላ ዘላ ከመሬት” እንዲሉ ወደ አባቶቻችን የሚስጢር እና ቅኔ ጉድጓድ መመለስ በንፅፅር ቀላል ነው፡፡ ወደ ድግምቱ … ምቀኝነቱ … መተቱ፡፡

 

Published in ባህል

*መጠለያው ሲሰራ ሁሉም ይሰጣቸዋል ማለት አይደለም፤ ይገባቸዋል ያልናቸውን ለይተናል
*ወረዳው ለትራንስፖርት ያወጣውን ገንዘብ ከፍለው እቃቸውን መውሰድ ይችላሉ

ባለፈው ሳምንት “ትራሳቸውን ቤተመንግስት ፤ ግርጌያቸውን ሸራተን ያደረጉ ቤት አልባዎች” በሚል ርዕስ በሸራተን አካባቢ ለመልሶ ማልማት በታጠረው ቤተ-መንግስቱ ሥር ባለው ቦታ በላስቲክ ቤት ውስጥ ስለሚኖሩ 48 አባወራዎችና ቤተሰቦቻቸው አስከፊ ህይወት ሰፋ ያለ ዘገባ ማቅረባችን ይታወሳል፡፡ በወቅቱ የወረዳውን ሃላፊዎች ማግኘት ባለመቻላችን በጉዳዩ ዙሪያ ምላሻቸውን ማካተት አልቻልንም፡፡ በዚህ ሳምንት የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ተስፋዬ ፣በአራዳ ክፍለ ከተማ የወረዳ ስምንት ዋና ስራ አስፈፃሚ ወ/ት ህይወት ጉግሳን አነጋግራ የሰጡትን ምላሽ አቅርበናል፡፡


በወረዳችሁ 48 አባዎራዎች ከነቤተሰባቸው ቤተመንግሥቱ ሥር በላስቲክ ቤት ውስጥ እንደሚኖሩ ታውቃላችሁ?
እናውቃለን፡፡ ቁጥራቸው ከ48 አባወራዎች ይበልጣል የሚል ግምትም አለን፡፡
እነዚህ ሰዎች በቀድሞው ቀበሌ 22 ውስጥ ከ17-23 ዓመት መኖራቸውንና ቦታው ለልማት ሲፈለግ ቤት አልባ እንደሆኑ ገልጸውልናል፡፡ የቀበሌ መታወቂያ ያላቸውም አሉ፡፡ የእነዚህ ሰዎች እጣ ፈንታ ምንድን ነው?
በመነሻነት ሁሉም ህጋዊ ባለይዞታዎች አልነበሩም፡፡ ቦታው ለመልሶ ማልማት ሲፈለግ ምትክ የሚሰጠው ባለይዞታ ለነበሩ ሰዎች ነው፡፡ ይህን የመልሶ ማልማት መመሪያን በተከተለ መልኩ ለባለይዞታዎች ምትክ ቦታ ሰጥተን አጠናቀናል፡፡
ታዲያ እነዚህ ነዋሪዎች ለበርካታ ዓመታት የት ነው የኖሩት?
እነዚህ ሰዎች በጥገኝነትና በተከራይነት አብረው የኖሩ ናቸው፤ ለምሳሌ በአንድ ቤት ቁጥር ስሜ ተመዝግቦ ባለይዞታ ከሆንኩ ምትክ ቤቱን የማገኘው እኔ ነኝ፡፡ ከዚያ በኋላ ያከራየኋቸውንም ሆነ ያስጠጋኋቸውን አብሬ ይዤ መሄድ አለብኝ ማለት ነው፡፡ ከላይ እንደነገርኩሽ ወረዳው የመልሶ ማልማት ስራ የተከናወነበት እንደመሆኑ ምትክ ለሚሰጣቸው ምትክ ሰጥተን ጨርሰናል፡፡ አሁን በላስቲክ ቤት ውስጥ የሚኖሩት ከቤተሰቦቻቸው ጋር ይኖሩ የነበሩ ናቸው፡፡ ለምሳሌ አንድ ልጅ ከቤተሰቡ ይዞታ ጐን ላይ ትንሽ ቤት ይሠራና እዚያው አግብቶ ይወልዳል፣ ከዚያ ለእኔም ቤት ይገባኛል ይላል፤ ይሄ የማይሆን ነገር ነው፡፡ ወረዳው ይህን ሰው የሚያውቀው ከቤተሰቡ ጋር ነው፣ ስለዚህ ቤተሰቡ ቤት ሲያገኝ አብሮ መሄድ ነው ያለበት፡፡
ወረዳው ታዲያ እነዚህ ዜጐች ምን እንዲሆኑ ያስባል?
እኛ ከፖሊስ ጋር ጭምር እየገባን እርምጃ ለመውሰድ ሞክረናል፣ ምክንያቱም ቦታው ለፀጥታ ስጋት እስከመሆን ደርሷል፡፡
ምን አይነት እርምጃ?
ከቦታው እንዲነሱና ወዳስጠጓቸው ወይም ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲቀላቀሉ ለማድረግ ሞክረናል፡፡ ቀደም ሲል እንደነገርኩሽ፣ አንዳንዶቹ “እኛም ቤት እናገኛለን” በሚል ከቤተሰቦቻቸው ተነጥለው የቀሩ ናቸው፡፡ ቤት ላንሰጣቸው፣ህጋዊ ባለይዞታ ላይሆኑ፣ ላስቲክ ወጥረው መኖርና መስራት እየቻሉ ወደ ልመና ማዘንበል አግባብ ነው ብሎ ወረዳው አያምንም፡፡ አሁን ተጠግቶ ለሚኖርና 18 ዓመት ለሞላው ሁሉ ቤት ለመስጠት የምንችልበት ደረጃ ላይ አይደለንም፡፡ በነገራችን ላይ በፊት በላስቲክ ቤት የሚኖሩት እነዚህ ብቻ አልነበሩም፤ በጣም ከፍተኛ ችግር ላለባቸው፣ የነበሩበት ሁኔታ በነዋሪዎች ኮሚቴና በአስተዳደር አካላት ተጣርቶ በተወሰነ መልኩ እንዲስተናገዱ ተደርጓል፡፡
በምን መልኩ ተስተናገዱ? ቁጥራቸውስ ምን ያህል ነው?
ቁጥራቸውን እርግጠኛ ባልሆንም ከ25 በላይ የሆኑና አደጋ ላይ ሊወድቁ ይችላሉ ተብለው የተመረጡ ሰዎች፣ የቀበሌ ቤትና መጠለያ ተሰርቶላቸው መፍትሔ አግኝተዋል፡፡ አሁን ያሉትን ሁሉ ለማስተናገድ ከአቅም በላይ ነው፡፡ በእርግጥ ቦታው ላይ ሆነሽ ስታያቸው፣ ህይወታቸው ሊያሳዝን ይችላል፡፡ ግን ቤተሰብ ስለሆኑ ብቻ ቤት ልስጥ ማለት አይቻልም፡፡ መመሪያ መጠበቅ አለበት፡፡
ባለይዞታ ባይሆኑም በስማቸው ቤት ባይኖራቸውም ቀደም ሲል ግን እዚሁ ቀበሌ ውስጥ የሚኖሩ ነበሩ፡፡ እንደዜግነታቸው መፍትሔ አያሻቸውም?
በነገራችን ላይ ለእነዚህም መፍትሔ እየተፈለገላቸው ነው፡፡ ቦታ ያልተሰጣቸው ህጋዊ ስላልሆኑ ነው፡፡ ለረጅም ጊዜ ኖረናል ይላሉ፣ ግን ሲኖሩ የነበረው ቀደም ሲል በነገርኩሽ አግባብ ነው፡፡ ከቤተሰባቸው ቤት ጐን ጠግነው፣ ተከራይተውና ተጠግተው ማለት ነው፡፡ እነዚህን ነገሮች ሁለት ሶስት ጊዜ አጣርተናል፡፡ “ወረዳው ነው የከለከለን፣ ክፍለከተማው ጉዳያችንን ይይልን” ብለው ወደ ክፍለ ከተማ ሄደው፣ ኮሚቴ ተዋቅሮ ጉዳዩ ታይቷል፡፡ ክፍለከተማውም ያገኘው ከእኛ መረጃ ውጭ አይደለም፡፡ አንድም እናትና አባቱ ሄደው ልጅ ነው የቀረው፡፡ እናም ወልጃለሁ፣ ቤተሰብ አለኝ ቤት ይገባኛል ነው የሚለው፣ አሊያም እንደአቅሜ በ30 ብር ተከራይቼ ረጅም አመት ኖሬያለሁ የሚሉ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች በአነስተኛና ጥቃቅን ተደራጅተው ስራ በመስራት፣ ኑሯቸውን እንዲለውጡ ወርደን እስከማማከር ደርሰናል፡፡ ከዚህ ውጪ ምትክ ቤት የምንሰጥበት አግባብ የለም፡፡ መመሪያውም ህጋዊ ተነሺዎች ስላልሆኑ አይደግፋቸውም፡፡
እነዚህ ሰዎች ግን በጊዜው ወደ ወረዳው እየመጡ አቤቱታ ሲያሰሙ “ቤት እንሰራላችኋለን” እንዳላችኋቸውና ለዚህም የማረጋገጫ ወረቀት እንደተሰጣቸው ይናገራሉ፡፡ እንዴት ነው?
ደብዳቤ ተሰጥቶናል የሚሉት ፍፁም እውነት ያልሆነና የተሳሳተ መረጃ ነው፡፡ እንሰራላችኋለን ብሎ ቃል የገባላቸው ወይም ለዚህ ማረጋገጫ ደብዳቤ የሰጣቸው አካል የለም፡፡ በእርግጥ በአንድ ወቅት “ስራ አጥ ስለመሆናችን ደብዳቤ ስጡን” ብለው የተሰጣቸው ደብዳቤ እጃቸው ላይ አለ፡፡
የቤት እቃቸው፣ የልጆቻቸው ልብስ ሳይቀር ተጭኖ መጥቶ ወረዳው ግቢ ውስጥ ዝናብ እያበሰበሰው እንደሆነ እነዚህ ሰዎች ይናገራሉ፡፡ እኛም የተወሰነ እቃ እዚሁ ግቢ ውስጥ ተመልክተናል፡፡ የልጆች ልብስና የመመገቢያ እቃ አጥተው መቸገራቸውን ገልፀውልናል፡፡ ይሄስ እውነት ነው?
እቃቸውን በተመለከተ ትክክል ናቸው፣ እዚህ ቀበሌ ግቢ ውስጥ አለ፡፡ ግን ተነጥቀው አይደለም የመጣው፡፡ አሁንም እንወስዳለን ካሉ የሚከለክላቸው የለም፡፡ እቃቸው የተጫነበት ምክንያት በቦታው ሰፊ የፀጥታ ችግር ነበር፡፡ መነሻውም ቤት ካልተሰጠን አንለቅም የሚል ነው፡፡ በዚህ የተነሳ የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር ለማርገብ፣ ከፖሊስ ጋር በትብብር ቦታው ድረስ ወርደን አነጋገርናቸው፡፡ “ህጋዊ ባለይዞታ ባልሆናችሁበት አግባብ ምትክ ይሰጠን ማለት አትችሉም፣ እንደማንኛውም ችግረኛ መጠየቅ ካለባችሁ በረብሻ ሳይሆን ወጥታችሁ ነው መጠየቅ ያለባችሁ” የሚል አቅጣጫ ሰጠናቸው፣ ነገር ግን ከችግራቸው በመነሳት “ቤት ካልሰጣችሁን፣ እንዲህ ካላደረጋችሁልን፣ ከእቃችን ጋር እዚሁ አጥፉን፣ አንቀሳቀስም” የሚል ጫፍ ያዙ፡፡ አሁን እንኳን ሄደን ብናናግራቸው ከዚህ የተለየ ነገር አይሉም፡፡
እኮ ከዚህ ወጥተው የት ይሂዱ? ወረዳውስ ምን አማራጭ አስቀመጠላቸው?
ወረዳው ህጋዊ ባለይዞታ ላልሆኑ አማራጭ የማስቀመጥ ግዴታ የለበትም፡፡ መመሪያውም ይህን አይፈቅድም፡፡ በዚህ የተነሳ እቃ ሊያነሱ አልቻሉም፡፡ ጭራሽኑ የበለጠ ያደራጁ ጀመር፡፡ እኛ ደግሞ መሬቱን ለመሬት ልማት ባንክ ማስረከብ ነበረብን፡፡ ምክንያቱም ቦታው ለገዛው ባለሀብት ስለሚውል ማለት ነው፡፡ እነሱ ግን ብዙ ቤተሰብና እቃ በመሰብሰብ ቤት እናገኛለን የሚል ወደ የዋህነት ያዘነበለ አስተሳሰብ ይዘዋል፡፡ ይህ ደግሞ የትም አያደርሳቸውም፡፡ በዚህ ምክንያት እቃቸውን ጭነን ወስደናል፡፡
ቀደም ሲል መውሰድ ከፈለጉ አሁንም መውሰድ ይችላሉ ብለሻል፡፡ መጀመርያ ለምን ተወሰደ? ይውሰዱ ከተባለስ--- “ውሃ ቅዳ ውሀ መልስ” ለምን አስፈለገ?
እንደነገርኩሽ ቦታውን ማስለቀቅ ነበረብን፡፡ እቃቸው ሲወሰድ ይነሳሉ በሚል ነበር የተጫነው፡፡ እነሱ ሊለቁ አልቻሉም፡፡ ሆኖም በጣም አስፈላጊ አስፈላጊ እቃዎችን፣ አንገብጋቢ ለሆነ ችግር የሚፈልጉትን እየመጡ እንዲወስዱ ነገርናቸው፣ እየወሰዱም ነው፡፡ ሙሉ እቃቸውን መውሰድ ከፈለጉ ግን ወረዳው ለትራንስፖርት ያወጣውን ወጪ ከፍለው መውሰድ ይችላሉ፡፡ የመጫኛ ጉልበት ራሳቸው ስለጫኑ አናስከፍላቸውም፡፡
እቃቸው ተጭኖ መወሰዱ ምን መፍትሄ አመጣ?
በወቅቱ መፍትሄዎችን አግኝተናል፡፡ ለምሳሌ እቃቸውን በማንሳታችን ምክንያት ቦታውን ለማስረከብ ስንነሳ፣ የወጠሩትን ላስቲክ ብቻ ለማፍረስ ቀላል ሆኖልናል፡፡
ማፍረስ ብቻ ሳይሆን ለስምንት ጊዜ ያህል ላስቲክ ቤቱን አቃጥላችኋል፣ ስታቃጥሉም ከሌሊቱ ስምንትና ዘጠኝ ሰዓት እየሄዳችሁ እንደሆነ ሰምተናል፡፡ ያንን ስታደርጉ ህይወት ቢጠፋ ንብረት ቢወድም ተጠያቂው ማን ነበር?
የላስቲክ ቤት ቃጠሎው የተካሄደው እነሱ ላይ ጉዳት በሚያደርስ መልኩ አይደለም፡፡ ከሌሊቱ ስምንት ዘጠኝ ሰዓት አቃጠሉብን የሚለው የተሳሳተ መረጃ ነው፡፡ ምክንያቱም የመንግስት የስራ ሰዓትም አይደለም፡፡ ከጠዋቱ 2፡30 እስከ 11፡30 ባለው ነው የምንሰራው፡፡ ሌላው ቀርቶ 12 ሠዓት ላይ እንኳን ሄደን አናስጨንቃቸውም፡፡ ሶስት አራት ጊዜ ወርደን አቃጥለናል፡፡ ትክክል ነው፡፡ በትክክል ካሰብነው ያሉበት ቦታ ለራሳቸው ለጤናቸውም አስቸጋሪ ነው፡፡
ግን እኮ ወደው አይመስለኝም ፡፡ አማራጭ ስላጡ ነው፡፡ ድሮ እነዚህ ሰዎች በ30 ብር ቤት ኪራይ ያገኙ ነበር፡፡ አሁን በ400 ብርም የለም፡፡ እንዴት ይሁኑ?
ልክ ነው ግን ከላስቲክ ቤቱ ቃጠሎ ለመጀመር፣ መጀመሪያ በአግባቡ ተነግሯቸዋል፣ ህጋዊ ባለይዞታ ስላልሆኑና እንዲህ አይነት ድርድርም ውስጥ መግባት ስለሌለብን፣ አስጠንቅቀን ጉዳት ሳይደርስባቸው ነው ያደረግነው፡፡ ይሄ በህግና በመመሪያ የሚተዳደር አገር ነው፣ ነገ ሌሎች የልማት ቦታዎች ላይ ሄደው ሰፍረው “አንወጣም ግደሉን” ማለት ይመጣል፡፡ ስለዚህ ቃጠሎው ከመምጣቱ በፊት ሶስትና አራት ጊዜ መድረክ ተመቻችቶ በደንብ ተነግሯቸዋል፡፡ ግን ሊሠሙ አልቻሉም፡፡ በዚህ የተነሳ ቃጠሎውን አከናውነናል፡፡ በሌሊት የተባለው ውሸት ነው፡፡ በሰው ላይ ጉዳት አላደረስንም፤ እኛ እንደውም ይህን ስናደርግ አማራጭ ዕድሎችን ይፈልጋሉ በሚል ነበር፡፡
ምን አይነት አማራጮችን?
ለምሳሌ አብዛኛው ወጣት ነው፤ የጉልበት ስራ፣ ኮብልስቶን፣ የብሎኬት ምርት ስራና በመሳሰሉት ተደራጅተው መስራትና የልመናን አስተሳሰብ ያስወግዳሉ፤ ከዚያም እንደየአቅማቸው ቤት ይከራያሉ ብለን ነበር፤ግን አልሆነም፡፡
መስራት የማይችሉ አቅመ ደካሞችና ህሙማን ጉዳይስ እንዴት ይታያል?
አቅመ ደካሞች ማለትም 70 እና 80 አመት የሆናቸው በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ሌላው ሰርቶ ለመኖር የሚያስችል አቅም አለው የሚል እምነት አለን፡፡ ይህን የፈጠረው ለስራ ያላቸው የወረደ አመለካከት ነው፡፡
ታዲያ ይህን የተዛባ አመለካከት የመቀየርና ህብረተሠቡን የማንቃት ሀላፊነት የማን ነው?
እኛ ብዙ ጊዜ ልናስተምራናቸው ሞክረናል ግን ወደ ልመና ያዘነብላሉ፡፡ ድሮም ተከራይተውና ተጠግተው ሲኖሩ ይሠሩ ነበር፤ አሁን እንደውም ከላይ የገለፅኳቸው አማራጭ ስራዎች አሉ፡፡ ከእነሱ መካከል ምክራችንን ሰምተው በብሎኬት ምርትና በኮብልስቶን የተሰማሩ አሉ፡፡ ወደፊትም አመለካከታቸውን ለመለወጥ ጥረታችንን አናቆምም፡፡
ቁርጥ ያለውን ንገሪኝ ፤ በአጭሩ ወረዳው እንደመፍትሔ የያዘው ሃሳብ አለው ?
አሁን ባለው ሁኔታ መንግስት ማንም ጐዳና እንዲወጣ አያበረታታም፤ እስከመጨረሻው የምንመክራቸው ወደ ቤተሰቦቻቸው ሊገቡ የሚችሉበት እድል ስላለ እሱን መጠቀም አለባቸው፡፡ ይህን በተጨባጭ ያውቃሉ፡፡ እኛም እናስተምራቸዋለን፡፡ ይሄ አንዱ ነው፡፡ ሁለተኛው፤አሁን መሬት ያልረገጠ ነገር ማውራት ጥሩ አይደለም እንጂ ጊዜያዊ ማረፊያ የማዘጋጀት ጉዳይ ለክፍለ ከተማው አቅርበን ሃሳቡ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ ሃሳቡ እንዴት ተግባራዊ እንደሚሆን እየታየ ነው፡፡ ወረዳው እንደ አጠቃላይ ሃሳብ ያየው ነገር፤ ህጋዊ ባለይዞታ አይደሉም፣ አዎ አይደሉም፣ ነገር ግን በቦታው ላይ በምንም መልኩ ቢሆን ልጅ ወልደው ቤተሰብ መስርተው በመኖራቸው ለማህበራዊ ቀውስ ተዳርገዋል ያላቸውን ሰዎች ለይቷል፣ በነገራችን ላይ ከነዚህ ሰዎች ጋር ቤት አገኛለሁ ብለው ከጐዳና ገብተው የተቀላቀሉም አሉ፡፡ የመፍትሔ ሃሳብ ስናዘጋጅ፣ በወረዳችን ክፍት የሆነ ቦታ እና ለጊዜያዊ መጠለያ ግንባታ ሊሆን ይችላል ያልነውን አየንና መነሻ ሃሳቡን ለክፍለከተማው አቀረብን፡፡ ክፍለከተማው፣ ወረዳው ያየበት አግባብ ጥሩ ነው በሚል ተቀብሎታል፡፡ ይህም ቢሆን በዜግነታቸው እንጂ በአሁኑ ወቅት መጠለያ የሚመከር ጉዳይ አይደለም፡፡ በዚህ ደረጃ ነው ያለው፡፡ ቦታው በመሀንዲሶች ይታያል፣ የግንባታው አይነትና ሁኔታ ምን ይምሰል የሚለው ይወሰናል፣ መሬቱ የሚፀድቅበት መንገድና አጠቃላይ ነገሮች ታይተው የሚሆነው ይሆናል፡፡
እነዚህ ሰዎች በዚህ ሁኔታ ህይወታቸውን መግፋት ከጀመሩ አምስተኛ አመታቸውን ይዘዋል፡፡ መጠለያውን ለማግኘትስ ምን ያህል ጊዜ ይወስድ ይሆን?
ቦታው ለልማት በአስቸኳይ ይፈለጋል፡፡ ቦታውን ለማስረከብ ደግሞ እነዚህን ሰዎች ቦታ ማስያዝ አለብን፡፡ ስለዚህ ከዚህ በኋላ ረጅም ጊዜ ይወስዳል ብዬ አላስብም፡፡ እዚህ ላይ ማስመር የምንፈልገው፣ ነገሩ እውን ሆኖ ጊዜያዊ መጠለያው ሲሰራ፣ እዚያ ያሉት ሰዎች ሁሉ ያገኛሉ ማለት አይደለም፣ ይገባቸዋል ያልነውን ለይተን አስቀምጠናል፡፡

Published in ህብረተሰብ

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

ኢድ-ሙባረክ! “ሃሎ!” “ሄሎ!” “ወ/ሮ በለጡን ነበር!” “ጌታዬ ተሳስተዋል፡፡” “ማን ልበል?” “ወ/ሮ በለጡ የሚባሉ በዚህ ስልክ የሉም!” ይሄ ቁጥር 091143…. አይደለም እንዴ!” “ነው፣ ግን እንደዛ የሚባሉ ሰው በዚህ ቁጥር የሉም፡፡” “እሺ አንተ ማነህ?” እናላችሁ…እንዲህ እንዲህ እያለ፣ ‘ጭቅጭቁ’ ይቀጥላል፡፡ ስሙኝማ…አንዳንዴ ሳስበው ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…ሰዉ “ተሳስተዋል…” ሲባል የማያምነው የመሸዋወድ ዘመን ስለሆነ ይመስለኛል። ልክ አንድ በኦፊሴል ያልተነገረ የብልጥነት ውድድር ውስጥ የገባን ነው የሚመስለው፡፡ አንድ ወዳጄ ሚኒባስ ውስጥ ያያት ጥቅስ ምን ትላለች መሰላችሁ… “ዶሮን ሲያታልሏት ውሀው የሚሞቀው ለገላሽ ነው አሏት!” አሪፍ አይደለች! እናማ ብዙ ነገር “ውሀው የሚሞቀው ለገላችሁ ነው…” አይነት እየሆነ ነው፡ እናላችሁ…ትክክለኛ መረጃ የሚሰጣችሁ ማግኘት አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡ ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ፣ ከዚህ በፊት ያነሳናት ነገር ትዝ አለችኝማ…በበፊት ጊዜ መሀል አራዳ ውስጥ ‘አራድነትን’ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ያደረሰ አንድ ሾተላይ ቢጤ ነበር፡፡ እናላችሁ…አውሮፕላን በሰማይ ሲያልፍ “አጎቴ እንዳያየኝ!” ምናምን ብሎ ሲኒማ ኢትዮዽያ ግንብ ላይ ይለጠፍ ነበር፡፡ ታዲያላችሁ…ዘንድሮ “አጎቴ እንዳያየኝ…” አይነት ‘ግንብ ላይ መለጠፍ’ ስለበዛ “ቁጥር ተሳስተዋል…” ሲባል ለመተማመን አስቸጋሪ እየሆነብን ነው፡፡

እናማ…ነገራችን ሁሉ ‘ጥብቅ ምስጢር’ አይነት ነገር ሆኗል፡፡ ምን ይገርመኝ ነበር መሰላችሁ…“ተሳስተዋል…” ሲባሉ የሚቆጡ ሰዎች መብዛት ይገርመኝ ነበር። ስታስቡት ግን ሁሉም ሰው “ተሳስተዋል…” ሲባል ግስላ ነገር የሚያደርገው ሁሉም ‘መጥፎ’ ወይ ‘ምግባረ ብልሹ’ ምናምን ስለሆነ አይደለም። ብዙዎቻችን በአንድም ምክንያት ይሁን በሌላ የውሸት ስም፣ የውሸት ስልክ ቁጥር፣ የውሸት አድራሻ መስጠት…የ‘ኑሮ በዘዴ’ ስትራቴጂ ምናምን ነገር አድርገነዋል፡፡ ነገርዬው…አለ አይደል….“ዋሸ ቢሉኝ እዋሻለሁ፣ ነፋስ በወጥመድ እይዛለሁ…” አይነት ነው፡፡ ከ‘ቦሶች’ እስከ እኛ ተራዎቹ ድረስ እውነት ያልሆነ መረጃ መስጠት እየተካንንበት የመጣ ነገር ነው። የሚያስፈራው ምን መሰላችሁ…ውሸት ሲነገር መሳቀቅ፣ አንደበትን ‘ያዝ፣ ያዝ’ ማድረግ… ምናምን ቀርቶ አንዲት የጸጉራችን ዘለላ ‘ሳትነቃነቅ’ መናገር መልመዳችን! የምር እኮ…እንደ ድሮ “እስቲ እጄን ምታ!” “እስቲ ይሄ ቀን አይንጋልኝ ብለሽ ማይ…” ምናምን አይነት ‘የማጣሪያ ጥያቄም ቀርቷል፡፡ ያውስ ‘መሀላ የምንፈራ’ ብንኖር አይደል! ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የስልክ ነገር ካነሳን አይቀር አስቸጋሪ ነገሮች አሉ፡፡ የኤቲክስ ምናምን ነገር “የጠላቶቻችን ሴራ…” ነገር እየመሰለ ነው፡፡ አሀ…ሁሉም ……. (እኔ የምለው…እግረ መንገዴን…እንደው ስትገቡ፣ ስትወጡ የእኛን የአዲስ አበቤዎችን ነገረ ሥራ እያያችሁልኝ ነው! በየእርስ በእርስ መአት ነገር እየተለወጠ አይመስላችሁም። አዲስ አበባ ውስጥ ‘ኢንደስትርያል ሪቮሉሽን’ ተቀልብሶ ወደ ‘አግራርያን ሪቮሉሽን’ እየተለወጠ ነው እንዴ! ቂ…ቂ…ቂ… አሀ…ግራ ሲገባንስ!) እኔ የምለው…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ስለ ስልክ ካነሳን አይቀር ደግሞ ሌላ አለላችሁ፡፡

አንዳንዱ ሰው ደግሞ ማንነታችሁን ገና ሳያረጋግጥ ይለቀቅባቸኋል፡፡ ስልኩን ሲጠራ ታነሱታላችሁ… “ሄሎ!” “አንተ ምን የማትረባ ሰው ነህ!” “አቤት፣ ማን ልበል?” “የማትረባ! ባንተ ቤት ብልጥ መሆንህ ነው!” “ጌታዬ የደወሉት ቁጥር…” “ስማ፣ እኔ… አይደለም የአንተ አይነቱን…” እናላችሁ…ፋታ ሳይሰጣችሁ ያለ የሌለውን ያወርድባችኋል፡፡ ታዲያላችሁ…እንደምንም ብላችሁ አንቱታን ወደ አንተ አውርዳችሁ… “ወንድም የተሳሳተ ቦታ የደወልክ መሰለኝ…” ትሉታላችሁ፡፡ “ወንድይፍራው አይደለህም!” “አይደለሁም…” ጥርቅም! ይቅርታ የለ፣ ምን የለ…ይጠረቅመዋል እናማ… እንዲህ አይነት ዘመን ውስጥ ደርሰንላችኋል! መከባበር ቀስ በቀስ እየተሸረሸረ፣ የሚያስተሳስሩን ማህበራዊ እሴቶች እየተበጣጣሱ አይደለም ታላቅ ሲመጣ ከወንበር ብድግ ማለት… መንገድ ላይ ትከሻ ገጭቶ እንኳን “ይቅርታ!” ለማለት “ኮሚሽን ይከፈለኝ…” የምንል ነው የሚመስለው፡፡

ስሙኝማ…ይሄ ‘ደረት ገልብጦ በአደባባይ የመዋሸት ልማድ’… አለ አይደል… ትውልድን እንዳያበላሽ አያስፈራችሁም! “ልጆች ምን እየሰሙ፣ ምን እያዩ እንደሚያድጉ አያሳስባችሁም! ውሽሚት ዘንድ ከትሞ ቡላ በቅቤውን እየላፈ ለሚስቱ “ፊልድ ለሥራ ሄጃለሁ…” የሚል አይነት ሽወዳ የሚሸውድ አባወራ በበዛበት አገር፣ “የት ይደርሳሉ…” የተባሉ ቤተሰቦች በውሸት ምክንያት እየተሰነጣጠቁ በምናይበት ዘመን…አለ አይደል…ለትውልድ የማንሰጋሳ! የባልና ሚስት ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…ሰዉ ለጸሎት ተሰብስቦ ተቀምጧል አሉ። እናማ…ድንገት ዲያብሎስ ፊት ለፊታቸው ድንቅር ይላል፡፡ የዚህን ጊዜ ሰዉ ሁሉ እየተጯጯኸ ወደ ቀረበው አቅጣጫ ይበራል፡፡ በዚህ ሁሉ ትርምስ መሀል ግን አንድ ሰውዬ ምንም ሳይንቀሳቀሱ ዝም ብለው ተቀምጠዋል፡፡ ዲያብሎስ ሆዬ ሰዉ ሁሉ ፈርቶት ሲራወጥ ሰውየው ምንም እንዳልተፈጠረ ነገር በዝምታ መቀመጣቸው ያበሽቀዋል፡፡ ይቀርባቸውናም… “እኔ ማን እንደሆንኩ አታውቅም እንዴ?” ይላቸዋል፡፡ “በደንብ አበጥሬ ነው የማውቅህ…” ይሉታል፡፡ “እና… እኔን አትፈራኝም ማለት ነው?” “ቅንጣት ታህል አልፈራህም…” ይሉታል፡፡ ይሄኔ ዲያብሎስ ግራ ይገባዋል፡፡ በብሽቀትም… “ዲያብሎስ ሆኜ እንዴት ነው የማትፈራኝ!” ይላቸዋል፡፡

እሳቸው ምን አሉ መሰላችሁ…“አውቅሀለኋ! ላለፉት ሀያ ዓመታት ከእህትህ ጋር በትዳር እየኖርኩ ነው…” አሉት ይባላል፡፡ እናላችሁ…የማወቅ ያለማወቅ፣ የመብሰል ያለመብሰል፣ በሥነ ምግባር የመታነጽ ያለመታነጽ … ምናምን ነገር ቀርቶ…መሀል ላይ ያሉ መስመሮች ሁሉ ጠፍተው…ሁላችንም አንድ ሳጥን ውስጥ ስንገባ አሪፍ አይደለም፡፡ ሴትዮዋ ሰዎችን ለእራት ጋብዛለች፡፡ የተጋበዙትም በምግብ ጠረዼዛ ዙሪያ ይቀመጣሉ፡፡ ሴትዮዋም የስድስት ዓመት ልጇን “ሚሚዬ፣ ጸሎት አድርጊልና…” ትላታለች፡፡ ሚሚም “እማዬ ምን እንደምል አላውቅም…” ትላታላች፡፡ እናትም “እኔ ስጸልይ የነበረውን ሰምተሽ የለ…እሱን በይ…” ትላታለች፡፡ ሚሚም ምን ብላ ጸለየች መሰላችሁ…“ጌታዬ ምን ሲያቀብጠኝ ነው ይሄን ሁሉ ሰዎች የጋበዝኩት!” የህጻናትን ንጹህ አእምሮ ለሁላችን ያድለንማ! ደህና ሰንበቱልኝማ!

Published in ባህል

*ግብረሰዶማዊያን በኢትዮጵያ ውስጥ “ሬንቦ” የተባለ ማህበር አቋቁመዋል
*በግብረሰዶማውያን ዙርያ የተካሄዱ ጥናቶች አዳዲስ መረጃዎችን ይፋ አድርገዋል
*ከ14 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናትና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የጥቃት ሰለባ ሆነዋል
*ኢትዮጵያውያን ከተመሳሳይ ፆታ ጋር ወሲብ ሲፈፅሙ የሚያሳዩ ፊልሞች ለገበያ ቀርበዋል

 ከወራት በፊት እዚህ አዲስ አበባ ከተማችን ውስጥ የተፈፀመ ታሪክ ነው፡፡ ድርጊቱ የተፈፀመው በአንድ ስመ-ጥር የወንዶች ልብስ መሸጫ ቡቲክ ውስጥ ነው፡፡ ወጣቱ በቡቲኩ ውስጥ ተቀጥሮ መስራት ከጀመረ ቆየት ብሏል፡፡ በአለባበሱ ሽቅርቅርና ዘመናዊ ነው፡፡ ወደ ቡቲኩ የሚመጡትን ደንበኞች በፈገግታና በትህትና እየተቀበለ ያስተናግዳል፡፡ ደንበኞች የፈለጉትን ልብስ አስወርደው ለመለካት ወደ መልበሻ ክፍል ሲገቡ በዓይኑ ይከተላቸዋል፡፡ በገቡበት የመልበሻ ክፍል መጋረጃ ላይ አይኖቹን ተክሎ ለደቂቃዎች እንደሚቆይ የቡቲኩ ባለቤት ብዙ ጊዜ ታዝቦታል፡፡ ሆኖም ደንበኞቹ አዲሱን ልብስ ለብሰው ሲወጡ ለማየት ከመጓጓት የተነሳ እየመሰለው በዝምታ ያልፈዋል፡፡ “ለምን እንዲህ ታያለህ?” ብሎ ጠይቆት አያውቅም፡፡ 

አብዛኛዎቹ የቡቲኩ ደንበኞች ወንዶች ናቸው፡፡ እጅግ ጥቂት ሴቶች፤ ለፍቅረኞቻቸው፣ ለባሎቻቸውና ለወንድሞቻቸው ልብስ ለመግዛት አሊያም ለማጋዛት ካልመጡ በቀር የሴት ዘር ወደ ስፍራው ዝር አይልም፡፡
የቡቲኩ ባለቤት አብዛኛውን ጊዜ ከቡቲኩ አይጠፋም፡፡ አልፎ አልፎ ከውጪ የመጡ ዕቃዎችን ለመረከብ፣ ክፍያ ለመፈፀምና መሰል ለሆኑ ጉዳዮች ወጣ ማለቱ ግን አይቀርም፡፡ የቡቲኩ ባለቤት ከወራት በፊት ተመሳሳይ ጉዳይ ገጥሞት ነው ቡቲኩን ለሰራተኛው ትቶለት የሄደው፡፡ ባለቤቱ ከሄደ በኋላ ዕድሜው በሃያዎቹ መጀመሪያ ላይ የሚገመት አንድ ወጣት ልብስ ለመግዛት ወደ ቡቲኩ ገባ፡፡ የቡቲኩ ሰራተኛ አይኑን ወጣቱ ላይ ተከለ፡፡ ወጣቱ ረዘም፣ ቀጠን ያለና ያለ ዕድሜው የተንቀዋለለ አይነት ነው፡፡ የሚፈልገውን ጅንስ መረጠና ወደ መለኪያ ክፍሉ ገባ፡፡ የቡቲኩ ሰራተኛ ጊዜ አላጠፋም፡፡ የቡቲኩን በር ከውስጥ ቆልፎ ወደ መለኪያው ስፍራ ሄደና መጋረጃውን ገለጠው፡፡ ወጣቱ ከለበሰው የውስጥ ሱሪ በስተቀር ከወገቡ በታች እርቃኑን ነበር፡፡ ሊለካው በያዘው ጅንስ ሱሪ አፉን አፈነው፡፡ ያላሰበው ነገር የገጠመው ወጣት፤ ለመጮህ፣ ለመታገልም ሆነ ለማምለጥና ለመከላከል አቅም አልነበረውም፡፡ እንደ ብረት ጠንክሮ ከያዘው እጅ ለማምለጥ በሞት ሽረት ትግል ቢፍጨረጨርም አልሆነለትም፡፡ እዛው የልብስ መለኪያ ክፍል ውስጥ አስገድዶ ደፈረው፡፡
የቡቲኩ ባለቤት ከጉዳዩ ተመልሶ ሱቁ ሲደርስ ቡቲኩ ያለወትሮው ተዘግቷል፡፡ ሁኔታው ያልተለመደ በመሆኑ ቡቲኩን በራሱ ቁልፍ ከመክፈቱ በፊት ጉዳዩን ለፖሊስ አመለከተ፡፡ ፖሊሶች በስፍራው ደርሰው በሩ ሲከፈት ተገድዶ የተደፈረው ወጣት፤ እዛችው የልብስ መለኪያ ክፍል ውስጥ በትውከትና በሰገራ ተጨማልቆ ወድቋል፡፡ ሌላ በቡቲኩ ውስጥ የተገኘ ሰው ግን አልነበረም፡፡ ባለቤቱ በሁኔታው እጅግ ደነገጠ፡፡ ፖሊሶች እሱን በቀጥጥር ስር አዋሉና ወጣቱን ወደ ህክምና ሥፍራ ላኩ፡፡ የቡቲኩ ባለቤት የሠራተኛውን ባህሪና ለደንበኞቹ የነበረውን አቀባበልና ስሜት ቀስ እያለ ማስታወስ ጀመረ፡፡ እንዴት ይህንን ነገር ሳልጠረጥር ቀረሁ ሲልም ተቆጨ፡፡ ግን ሁሉም ነገር ጅብ ከሄደ---- ሆኖበታል፡፡ ለቀናት በፖሊስ ጣቢያ ቆይቶ፣ በዋስ ተለቀቀ፡፡ ወንጀል ፈፃሚው ግለሰብ ግን ዛሬም ድረስ ዱካው አልተገኘም፡፡
እንዲህ ያሉ ታሪኮች ዛሬ በአገራችን በተለይም በመዲናችን የተለመዱ ተግባራት ሆነዋል፡፡ ድርጊቱ ከዕለት ወደ እለት እጅግ በሚዘገንንና በሚያስደነግጥ ሁኔታ እየተስፋፋ ነው፡፡ ህፃናት ልጆች በትምህርት ቤታቸው ውስጥ በሚያስተምሯቸው መምህራን እየተደፈሩ ነው፡፡
ለዚህ ደግሞ በፌደራሉ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ሰባተኛ ወንጀል ችሎት እየታየ ያለውና በ“ካራክተር ሆልማርክ አካዳሚ” መምህራን ተፈፀመ የተባለው የግብረሰዶም አስገድዶ የመድፈር ወንጀል የቅርብ ጊዜ አብነት ነው፡፡ ስድስት መምህራን የአስርና የአስራ አንድ አመት ዕድሜ ባላቸው ሁለት ህፃናት ላይ በተደጋጋሚ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ፈፅመዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸው፣ ጉዳዩ በክስ ሂደት ላይ ይገኛል፡፡
በአሁኑ ወቅት ድርጊቱ እጅግ እየተስፋፋ ሲሆን በማህበረሰቡም ላይ የስነ ልቦናና የማህበራዊ ግንኙነት እንዲሁም፣ የትምህርት ማቋረጥና የጤና ችግር እያስከተለ እንደሆነ በአዲስ አበባ ከተማ ሴቶችና ወጣቶች ቢሮ በቅርቡ የተደረገ ጥናት ይጠቁማል፡፡ ጥናቱ በአሁኑ ወቅት ተመሳሳይ ፆታን ለወሲብ ማሰብ እጅግ እየተለመደ መምጣቱንና ከተመሳሳይ ፆታ ጋር ወሲብ በመፈፀም ሥራ የሚተዳደሩ ሰዎች መበራከታቸውን ይፋ አድርጓል፡፡ የዚህ ችግር ሰለባዎች በአብዛኛው ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት፣ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች እንዲሁም የከፍተኛ ተቋማት ተማሪዎች፣ በወሲብ ንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎችና በማረሚያ ቤቶች ውስጥ የሚገኙ የህግ ታራሚዎች መሆናቸውንም ጥናቱ አረጋግጧል፡፡
የግብረሰዶማዊነት ችግር የምዕራባውያንና የሰለጠኑት አገራት ችግር ብቻ እንደሆነ መቁጠር፣ ህብረተሰቡን ለአስከፊ ጉዳት እንደዳረገው የጥናት ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡ ይሄ ዓይነቱ አዝማሚያ መዘነጋት በመፍጠር ወላጆች ስለ ልጆቻቸው አዋዋል፣ የባህርይ ለውጥና አለባበስ እንዳያስተውሉና ወቅታዊ እርምጃዎች እንዳይወስዱ ያደረገ ሲሆን ልጆችንም እጅግ ለከፋ ጉዳት እያጋለጠ ነው፡፡ ትናንት በሩቁ ስንሰማው የነበረው ግብረሰዶማዊነት፤ ዛሬ የእያንዳንዳችንን ቤት የሚያንኳኳ የሁላችንም ሥጋት ሆኗል፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት በ“ሴቭ ዘ ቺልድረን ካናዳ” እና በ“ብራይት ፎር ቺልድረንስ ቮለንተር አሶሴሽን” ትብብር የተካሄደ ጥናት እንዳመለከተው፤ በከተማችን አዲስ አበባ ከሚፈፀሙ የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች መካከል 22 በመቶ የሚደርሱት የተፈፀሙት በወንዶች ላይ ነው፡፡ እነዚህ ወንዶች የተደፈሩትም ተመሳሳይ ፆታ ባላቸው ሰዎች ነው፡፡ ጥቃቱ ከተፈፀመባቸው አብዛኛዎቹም ዕድሜያቸው ከ14 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት ናቸው፡፡ ከጥቃቱ ፈፃሚዎቹ መካከል 43.7 በመቶ ያህሉ የጥቃቱ ሰለባዎች የቅርብ ሰዎች እንደሆኑ ጥናቱ አመልክቷል፡፡
የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወጣቶች ማህበር ከክፍለ ከተማው ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር የግብረ ሰዶማዊነት መስፋፋትን ለማውገዝ ሰሞኑን አንድ ትልቅ ጉባዔ አዘጋጅቶ ነበር፡፡ በገነት ሆቴል በተዘጋጀውና በሺዎች የሚቆጠሩ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ታዋቂ የኪነጥበብ ባለሙያዎችና የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች በተገኙበት በዚህ ጉባዔ ላይ “ዩናይትድ ፎር ላይፍ ኢትዮጵያ” በተባለ አገር በቀል መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት የተዘጋጀ ጥናታዊ ፅሁፍ ቀርቧል፡፡ የድርጅቱ መሥራችና ዳይሬክተር ዶ/ር ሥዩም አንቶኒዮስ በዚሁ ጥናታቸው ላይ እንደገለፁት፣ ግብረሰዶማዊነት በአገሪቱ እጅግ በጣም በሚያስደነግጥ ሁኔታ እየተስፋፋ ነው፡፡
የመጀመሪያና የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የግብረሰዶማውያን መፈልፈያ ቦታዎች እየሆኑ ነው፡፡ በአንድ መንግስታዊ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ውስጥ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ፣ በሴቶች የመኝታ ክፍሎች (ዶርም) ውስጥ ከ130 በላይ የተለያዩ አርቴፊሻል የወሲብ መሣሪያዎች ተገኝተዋል፡፡ እዚሁ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚገኝ አንድ የኮንዶሚኒየም ህንፃ ውስጥ አንድ የአስራ ሰባት አመት ወጣት በርካታ ወንድ ህፃናትን እያባባለና እያስገደደ ደፍሯል፡፡ በከተማውም ሆነ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የግብረሰዶም ተግባር እጅግ በሚያስደነግጥ ፍጥነት እየተስፋፋ መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር ሥዩም፣ ከአዲስ አበባ ከተማ ውጪ በተለያዩ ጊዜያት በወንዶች ፊንጢጣ ውስጥ ገብተው የቀሩ የለስላሳ ጠርሙስና ሌሎች ባዕድ ነገሮች በቀዶ ጥገና ወጥተዋል ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ወንዶች ከወንድ ጋር፣ ሴቶች ደግሞ ከሴቶች ጋር ወሲብ ሲፈፅሙ የሚያሳዩ ፊልሞች ተሠርተው ገበያ ላይ መዋላቸውንም ጠቁመዋል፡፡
በአገሪቱ የግብረሰዶማዊነት ተግባር እጅግ መስፋፋቱን አመላካች ከሆኑት ተግባራት መካከል ግብረሰዶማውያኑ “ሬይንቦ” የተባለ ማህበር በግልፅ አቋቁመው፣ አባላት ለመመልመልና ድርጊቱን ለማስፋፋት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ዶ/ር ሥዩም ተናግረዋል፡፡ ድርጊቱ በአገሪቱ እንዲበራከትና እንዲስፋፋ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል በSex tourism አማካኝነት ወደ አገራችን የሚገቡ የውጪ ዜጐች፣ ከኢትዮጵያ ውጪ ኖረው የሚመጡ ኢትዮጵያውያን፣ ወደተለያዩ አገራት ለንግድና ለሌሎች ሥራዎች የሚንቀሳቀሱ ሰዎች እና የልቅ ወሲብ ፊልሞች መበራከት እንደሆኑ ተጠቁሟል፡፡
አሁን በአገሪቱ ውስጥ ባለው ሁኔታ የሴት ግብረሰዶማዊያን (ሴት ለሴት ግንኙነት የሚፈፅሙ) በቁጥር አነስተኛ መሆናቸውን የገለፁት ዶ/ር ሥዩም፣ የወንድ ግብረሰዶማውያን ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ ነው ብለዋል፡፡ በሆነ አጋጣሚ ወይም በመደፈር ወደ ግብረሰዶማዊነት ህይወት የሚገቡ ወጣቶች ወይም ህፃናት ድርጊቱን እንዳያቆሙና ከችግራቸው እንዳይላቀቁ ግብረሰዶማውያኑ ያስፈራሯቸዋል - “አንድ ጊዜ በፊንጢጣ ግንኙነት ማድረግ ከጀመርክ ፊንጢጣ ውስጥ የሚፈጠር እጭ ይኖራል፡፡ እጩ ደግሞ በየጊዜው ስፐርም ማግኘት ይኖርበታል፣ ያለዚያ ግን አንጀትህን ይቦድሰውና ለከባድ የጤና ችግር ትጋለጣለህ” እያሉ፡፡ በዚህ ምክንያትም አንድ ጊዜ የችግሩ ሰለባ የሆኑ ሰዎች ከድርጊቱ ለመላቀቅና ወደ ትክክለኛው ህይወት ለመመለስ አይፈልጉም፡፡ ይህ አባባል ግን ፈፅሞ ከእውነት የራቀና ግብረሰዶማውያኑ የአባላት ቁጥራቸውን ለማበራከት የሚጠቀሙበት ዘዴ ነው ብለዋል፡፡ ህብረተሰቡ ይህንን እጅግ አደገኛ በሆነ ፍጥነት እየተስፋፋ ያለውን የግብረሰዶማዊነት ተግባር ለመግታት ከፍተኛ ንቅናቄ ማድረግ እንደሚገባውና እያንዳንዱ ሰው በቤቱ ውስጥ በልጆቹ ላይ የሚታዩ ለውጦችን ትኩረት ሰጥቶ በመከታተል፣ ልጆቹ ወደማይመለሱበት ጥፋት ውስጥ ከመግባታቸው በፊት ሊታደጋቸው ይገባል ሲሉ ዶ/ር ሥዩም ተናግረዋል፡፡
ግብረሰዶማውያን በከተማዋ የተለያዩ ቦታዎች የራሳቸው መገናኛ ሆቴሎች፣ መቀጣጠሪያ ካፌዎች፣ የተመሳሳይ ፆታ ወሲብ መፈፀሚያዎች፣ መዝናኛና ማሣጅ ቤቶች እንዳሏቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከተመሳሳይ ፆታ ጋር ወሲብ በመፈፀም ሥራ የሚተዳደሩ ግብረሰዶማውያን (ቆሚታዎች ነው የሚባሉት) በአብዛኛው በቦሌ አካባቢ የሚገኙ ሲሆን በተለይ ደግሞ ፍሬንድሺፕ ህንፃ፣ ቦሌ ድልድዩ አጠገብና፣ ቦሌ ሸዋ ዳቦ አካባቢዎች ይጠቀሳሉ፡፡ ፒያሣ የሚገኙ ጥንታዊ ሆቴሎችና ረዘም ያለ ዕድሜን ያስቆጠረ አንድ ካፌም የግብረሰዶማውያን መገናኛ፣ መቀጣጠሪያና መተዋወቂያ ሥፍራዎች ናቸው፡፡ ከጥናቱ ለመረዳት እንደተቻለው፣ ግብረሰዶማውያኑ አብዛኛውን ጊዜ ከተለመዱት የወንዶች አለባበስና ስታይል ለየት ያሉና በቀላሉ አይን የሚስቡ ነገሮችን ማድረግ የሚያዘወትሩ ሲሆኑ አብዛኛዎቹ በግራ ጆሮአቸው ላይ ሎቲ ያደርጋሉ፡፡ ጠበብ ያሉ (ታይት) ሱሪዎችን፣ ሰውነትን በተለይም ደረትና ክንድን የሚያጋልጡ ልብሶችን መልበስና ሱሪያቸውን ዝቅ በማድረግ ፓንታቸውን እያሣዩ መሄድንም ያዘወትራሉ፡፡ ቅንድባቸውን ለመቀንደብ፣ ጥፍራቸውን ለመሞረድና የእግር ተረከዞቻቸውን ለመሠራት አብዛኛዎቹ ግብረሰዶማውያን የሴቶች የውበት ሳሎኖችን ያጣብባሉ፡፡ ብዙውን ጊዜም ነጣ ያሉ (ድፍን ነጭ) ካልሲዎችን በክፍት ጫማ ማድረግን ያዘወትራሉ፡፡ ሁልጊዜም ንፁህና መልካም ጠረን እንዲኖራቸው ይተጋሉ፡፡ በአዲስ አበባ የሚገኙ በርካታ ፔኒሲዮኖች ለግብረሰዶማውያን አገልግሎት በመስጠት ተግባር ላይ እንደሚሳተፉም ለማወቅ ተችሏል፡፡
ለግብረሰዶማውያንነት በአብዛኛው ተጋላጭ የሚሆኑት በወላጆቻቸው የተረሱ ህፃናት፣ ከአንድ ወላጅ ጋር ብቻ የሚኖሩ፣ የጐዳና ተዳዳሪዎች፣ ስደተኞች፣ የአዕምሮ ውሱንነት ችግር ያለባቸው ሰዎች፣ የአካል ጉዳተኞችና በህፃናት ማሳደጊያ ውስጥና በማረሚያ ቤቶች ውስጥ ያሉ ሰዎች መሆናቸው በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡ የግብረሰዶማዊነት ችግር ለኤችአይቪ፣ ለወሲባዊ ግንኙነት ፍላጐት ለማጣት፣ ራስን ለመጥላት፣ ከሰዎች ለመገለልና ለብቸኝነት፣ ለጭንቀትና ፍርሃት እንዲሁም ከአስራ አራት በላይ ለሚሆኑ የጤና ችግሮች እንደሚያጋልጥ ተገልጿል፡፡ ይህ ወቅታዊ ጥሪ ለወላጆች፣ ለመንግስትና ለህብረተሰቡ እንዲሁም ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት ሁሉ የቀረበ ሲሆን ጉዳዩ አፋጣኝ የመፍትሔ እርምጃ ካላገኘ እጅግ አደገኛ ለሆነ የማህበረሰባዊ ቀውስ ይዳርጋል፡፡

አንድ ባቡር በአንድ ጉዞ ከ300 በላይ ተጓዦችን ያሳፍራል
. ባቡሩ 80 ኪሎ ሜትር በሠአት የመብረር አቅም ይኖረዋል
. በአፍሪካ የከተማ ባቡር ተጠቃሚዎች ሰባት ብቻ ናቸው

የአዲስ አበባ ከተማ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት በሁለት ምዕራፎች ተከፍሎ የሚከናወን ሲሆን በጠቅላላው 32 ኪሎ ሜትር ገደማ የሚደርሠው የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ፣ በ2007 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል፡፡ ሁለተኛው ዙር ፕሮጀክት፤ የባቡር መስመር ዝርጋታውን ወደ 75 ኪሎ ሜትር የሚያደርስ ሲሆን ይህ የማራዘሚያ ፕሮጀክት የሚከናወነው በ2006 ዓ.ም ነው፡፡ 
አሁን በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኘው የመጀመርያ ምዕራፍ የባቡር መስመር ዝርጋታ መነሻው ሃያት ሲሆን በመገናኛ፣ 22፣ ኡራኤል፣ መስቀል አደባባይ፣ ሜክሲኮና ልደታ አድርጐ ጦር ሃይሎች የሚደርስና የ16.3 ኪ.ሜ ርዝመት ያለው ነው፡፡ ከሠሜን ወደ ደቡብ የሚጓዘው ደግሞ መነሻው ከፒያሣ (ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን) ሆኖ በአዲስ ከተማ፣ አውቶቡስ ተራና 7ኛ አድርጐ፣ ከጦር ሃይሎች ከሚመጣው መስመር ጋር በጥምረት እስከ መስቀል አደባባይ ከመጣ በኋላ እስከ ቃሊቲ ማሠልጠኛ አደባባይ የሚዘልቅና የ17.5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ነው፡፡
በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ኢ/ር በሃይሉ ስንታየሁ፤ ስለባቡር መስመር ዝርጋታው፣ ስለባቡሮቹ አቅምና የቴክኖሎጂ ደረጃ፣ እንዲሁም ስለፌርማታና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ተጠይቀው የሠጡትን ምላሽ ጠቅለል አድርገን በሚከተለው መልኩ አጠናቅረነዋል፡፡

የባቡሮች አቅም እና የአገልግሎት ዘመን
የፕሮጀክቱ ምዕራፍ አንድ ሲጠናቀቅ 41 ባቡሮች ወደ አገልግሎት ይሠማራሉ፡፡ አንድ ባቡር 3ዐ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን ይህም ማለት ከሁለት ባለ ተቀጣጣይ የቢሾፍቱ አውቶብሶች ርዝማኔ ላይ 6 ሜትር ብቻ መቀነስ ማለት ነው፡፡ የአንዱ ተቀጣጣይ አውቶቡስ ርዝመት 18 ሜትር ሲሆን የሁለት አውቶብሶች ሲደመር 36 ይሆናል፡፡ በባቡሩ ውስጥ 64 መቀመጫዎች ብቻ ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ወንበሮች ለአቅመ ደካሞችና ለአካል ጉዳተኞች እንዲሁም ለረጅም ርቀት ተጓዦች የተሠናዱ ሲሆን አብዛኛው ተጠቃሚ ቆሞ እንዲሄድ ይጠበቃል፡፡ በአንድ ካሬ ሜትር ውስጥ ከ6-8 ሠው ሊቆም ይችላል በሚል ሲሠላ፣ በአጠቃላይ አንድ ባቡር በአንድ ጉዞ ከ268 እስከ 317 ሠዎችን ማጓጓዝ ይችላል ማለት ነው፡፡ በዚህ አይነት በሁለቱ አቅጣጫ የሚጓዙት ባቡሮች፣ በጋራ በሚጠቀሙት ከልደታ እስከ መስቀል አደባባይ ባለው መስመር እስከ 15ሺህ ሠው በአንድ ሠአት ውስጥ ማጓጓዝ የሚቻል ሲሆን በተናጠል በሚጓዙባቸው መስመሮች ቁጥሩ እስከ 7ሺህ ይጠጋል፡፡
የባቡር መሠረት ልማቱ (ሃዲዱ) በየጊዜው ተገቢው ጥገና እየተደረገለት እስከ መቶ አመት ድረስ እንዲያገለግል ታስቦ ነው የሚሰራው፡፡ ከኤሌትክሪፊኬሽንና ሲግናል (ማመላከቻ) እንዲሁም ከዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ጋር የተያያዙት ደግሞ አስፈላጊው እድሣትና ጥገና እየተደረገላቸው እስከ 40 አመት እንዲያገለግሉ ተደርገው ይሠራሉ፡፡

የባቡር ፌርማታዎች
ከሰሜን ደቡብ፣ ከምስራቅ ምዕራብ በሚዘረጉት እያንዳንዱ መስመር 22 ፌርማታዎች የሚኖሩ ሲሆን በጠቅላላው 39 ፌርማታዎች ይዘጋጃሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ አምስቱ ከልደታ እስከ መስቀል አደባባይ በሚዘልቀው የጋራ መስመር ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ በየፌርማታዎቹ መካከል በአማካይ እስከ 700 ሜትር ርቀት የሚኖር ሲሆን በአንዳንድ ቦታ እስከ 400፣ ረጅም በሆኑት ለምሣሌ እንደጐተራ ማሳለጫ አካባቢ ደግሞ እስከ 1.2 ኪሎ ሜትር ርቀት ይኖራል፡፡ ተገቢው ፌርማታ ጋ ለመድረስ አንድ ተጠቃሚ ከ300 እስከ 400 ሜትር ብቻ በእግሩ መጓዝ ይጠበቅበታል ማለት ነው፡፡
ፌርማታዎቹ ሦስት አይነት ናቸው ይላሉ -ስራ አስኪያጁ፡፡ አንደኛው መሬት ላይ የሚሠራ ፌርማታ ነው፡፡ ሁለተኛው የድልድይ ላይ ፌርማታ ሲሆን ሦስተኛው የመሬት ውስጥ ፌርማታ ናቸው፡፡ የመሬት ላይ ፌርማታ በሚሆንበት ጊዜ፣ ተጠቃሚዎች ለዚሁ አገልግሎት ብቻ በሚሰራ 60 ሜትር በሚረዝም ወለል (ፕላት ፎርም) ላይ ሆነው ይጠብቃሉ፡፡
ጀድልድይ ፌርማታ ደግሞ ከድልድዮቹ በቀጥታ በግራና ቀኝ በኩል ወደ እግረኞች መንገድ ዳር የሚወርዱ የመተላለፊያ ደረጃዎችና ሊፍቶች ይኖራሉ፡፡ አንድ ሰው በድልድዩ ፌርማታዎች መጠቀም ከፈለገ፣ በአስፓልቱ ዜብራዎች በኩል በእግሩ ግራና ቀኝ አስፓልቱን አቋርጦ፣ ደረጃው ጋ ከደረሰ በኋላ ከፈለገ በደረጃው፣ ካሻውም በሊፍቱ ሽቅብ ወደ ድልድዩ መውጣት ይችላል፡፡ በተለይም አቅመ ደካሞችና አካል ጉዳተኞች ሊፍቱን እንዲጠቀሙ ቅድሚያ ይሰጣል፡፡
በመሬት ውስጥ ፌርማታዎችም በሁለቱም አቅጣጫ ወደ ውስጥ የሚያስገቡና የሚያስወጡ ደረጃዎች እና ሊፍቶች ይኖራሉ፡፡ በዚያ መሠረት ሁሉም ሰው የሚመቸውን አማራጭ በመጠቀም ወደ ውስጥ መግባትና መውጣት ይችላል፡፡

የባቡሮቹ ፍጥነትና የቴክኖሎጂ ደረጃቸው
የመጀመያው ምዕራፍ ግንባታ በ2007 ዓ.ም ከተጠናቀቀ በኋላ ወደ አገልግሎት ይገባሉ ተብለው የሚጠበቁት ባቡሮች፤ በሰአት 80 ኪሎ ሜትር የመብረር አቅም እንዲኖራቸው ተደርገው ዲዛይን የሚደረጉ ሲሆን ወደ አገልግሎት ሲሰማሩ ግን በአማካይ በየ700 ሜትር ርቀት ፌርማታ ስለሚኖር ፍጥነታቸው በሰአት ከ30 እስከ 40 ኪሎ ሜትር ዝግ እንዲል ይደረጋል፡፡ የቀላል ባቡር ፕሮጀክቱ በጀት የባቡሮቹን ዋጋም የሚያጠቃልል ነው፡፡ ኮንትራክተሩ ከመከላከያ ኢንጅነሪንግ ጋር በጋራ የሚገጣጥማቸውን ባቡሮች ጨምሮ ከውጭ ተገዝተው የሚመጡ ባቡሮችም ይኖራሉ፡፡
የቴክኖሎጂ ደረጃቸውን በተመለከተ አሁን የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት በተስፋፋባቸው ሃገሮች ያለውን የሲግናል (ማመላከቻ)፣ የኮሚኒኬሽንና የኤሌክትሪክፊኬሽን ሲስተም ያሟላ እንደሚሆን ኢንጂነር በኃይሉ ይገልፃሉ፡፡ ለምሳሌ የትኬት አገልግሎት ሲስተሙን ስንመለከት፣ ሁለት አይነት ትኬት ይኖራሉ፡፡ የኤሌክትሮኒክስ እና የወረቀት ትኬቶች፡፡ በዋናነት ጥቅም ላይ የሚውለው የኤሌክትሮኒክ ቲኬቱ ሲሆን ማንኛውም ባቡር ተጠቃሚ ያንን ትኬት ከኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ከገዛ በኋላ፣ በየጊዜው ሂሣብ እያስሞላ መጠቀም ይችላል፡፡ በየቦታው የተዘጋጁ የሂሳብ መሙያ ጣቢያዎችም ይኖራሉ፡፡ ተጠቃሚው ልክ ወደ ባቡሩ ሲገባ፣ በሩ ላይ ወደሚገኘው ትኬት አንባቢ መሣሪያ (SVT Reader) ቲኬቱን በማስጠጋት እንዲነበብለት ያደርጋል፡፡ በቂ ሂሣብ ካለው እንዲገባ ይፈቀድለታል፡፡ ይህን ሂደት የሚቆጣጠሩ መኮንኖችም በባቡሩ ውስጥ ይኖራሉ፡፡ ተጠቃሚው መውረጃው ጋ ሲደርስ በድጋሚ የኤሌክትሮኒክስ ትኬቱን በሩ ጋ ወዳለው አንባቢ መሣሪያ በማስጠጋት እንዲነበብና ለተጓዘባት ኪሎ ሜትር ተገቢው ክፍያ እንዲቆረጥ ያደርጋል፡፡ አንባቢ መሣሪያውም ተጠቃሚው የተጓዘበትን ርቀት አስልቶ ሂሣቡን ይቆርጣል፡፡ አንድ ተሣፋሪ ይህን ሳያደርግ ከወረደ፣ መሣሪያው እስከ መጨረሻው ፌርማታ ድረስ ያለውን ታሪፍ አስልቶ ይቆርጥበታል፡፡ በዚህ ሂደት የባቡሩ ሠራተኞች (መኮንኖች) የት ኬት ማንበቢያ መሣሪያውን በእጃቸው ይዘው ተገቢውን ቁጥጥርና ክትትል ያደርጋሉ፡፡
የወረቀት ትኬቱ በአብዛኛው ከክፍለ ሀገር ለሚመጡና የአጭር ጊዜ ቆይታ ላላቸው የአንድ ጊዜ ተጓዦች የሚዘጋጅ ይሆናል፡፡ የጉዞ ታሪፍ በተመለከተ አሁን የተወሰነ ነገር ባይኖርም የአብዛኛውን ህብረተሰብ አቅም ያገናዘበ ይሆናል ተብሎ ይገመታል፡፡
ባቡሩ ከትኬት አቆራረጥ ዘመናዊነቱ ባሻገር፣ የባቡሩን መነሻና መድረሻ እንዲሁም እያንዳንዱን የሚቆምበትን ፌርማታ ለተሳፋሪዎች በድምጽና በጽሑፍ ያሳውቃል፡፡
ለዚሁ በተዘጋጀው ስክሪን ላይ ቀጣይ ፌርማታ የቱ እንደሆነም ይገልፃል፡፡ በድምጽም ጭምር፡፡ በአሁኑ ወቅት የባቡር ኦፕሬተሮች፣ ቲኬተሮች፣ የቁጥጥር ባለሙያዎችና የመሳሰሉትን ለማሰልጠንም ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡

የባቡሩና የመኪኖች መንገድ አጠቃቀም
መኪናዎችና ባቡሩ በመስቀለኛ መንገዶች ላይ እንዴት ይተላለፋሉ ብለን የጠየቅናቸው ኢንጂነር በሃይሉ፤ የባቡሩ መስመር አይነት በከፊል የተዘጋ የሚባለው ሲሆን ራሱን ችሎ ከመኪና መንገድ ጋር ሳይገናኝ የመጓዙን ያህል በሌላ በኩል ከመኪኖች ጋርም መንገድ የሚጋራባቸው ጥቂት ቦታዎች እንደሚኖሩ ይናገራሉ፡፡ ባቡሩ ከመኪኖች ጋር ሊገናኝ የሚችለው ወደ ኋላ በሚመለስበት ጊዜና በመስቀለኛ መንገድ ላይ ነው፡፡ ባቡሩ ከመኪናዎች ጋር በሚቆራረጥባቸው የተወሰኑ ቦታዎች አካባቢ ሲደርስ፣ ከርቀት የሲግናል ማመላከቻዎች በመጠቀም መኪኖች በቀይ መብራት እንዲቆሙ ይደረጋል፡፡ ባቡሩ በፍጥነት ሲያልፍ ወዲያው መኪኖቹ ይለቀቃሉ፡፡
የአፍሪካ ሃገራት ልምድ ምን ይመስላል?
በአፍሪካ ውስጥ የቀላል ባቡር አገልግሎት የተስፋፋ አይደለም ይላሉ - ኢንጂነሩ፡፡ ከ54 የአፍሪካ ሀገራት መካከል የከተማ ባቡር ተጠቃሚ የሆኑትና ለመሆን እየሰሩ ያሉት ኢትዮጵያን ጨምሮ ሰባት ሀገራት ብቻ ናቸው፡፡ እነሱም የሰሜን አፍሪካ ሀገራት እና ደቡብ አፍሪካ ናቸው፡፡ ከሰሜን አፍሪካ የካይሮ ሜትሮ ባቡር ተጠቃሽ ነው፡፡
በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ልምድ የወሰደችበት የቱኒዚያ ቀላል ባቡር አገልግሎትም ተጠቃሽ ነው፡፡ በሌላ በኩል በአልጄሪያ፣ ሞሮኮ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ፣ ፕሪቶሪያ እና ኬፕታውን የተለያየ አይነት የከተማ ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት አለ፡፡ በግንባታ ላይ ካሉት ደግሞ በናይጄሪያ ሌጐስ እና አዲስ አበባ ላይ የተዘረጉት ፕሮጀክቶች ተጠቃሽ ሲሆኑ የአዲስ አበባው ከሰሃራ በታች ካሉ ሃገራት ቀዳሚው ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የባቡር መስመር ግንባታው ሂደት
በመሬት ላይ የሚገነባውና በድልድይ የሚገነባው የባቡር መስመር በጥሩ ሂደት ላይ ሲሆኑ እንደሆነ የሚናገሩት ኢንጂነር በኃይሉ፤ ከሁሉም የላቀ ስራ የተከናወነው በመሬት ውስጥ በሚገነባው የባቡር መስመር ነው ይላሉ፡፡
በድልድይ የሚገነባው መስመር ከወሰን ማስከበር ጋር በተያያዘ አንዳንድ ችግሮች እንዳጋጠሙት ግን አልሸሸጉም፡፡ በተለይ ከመስቀል አደባባይ እስከ ለገሃር ባለው መስመር ባለቤቱ የማይታወቅ ምናልባትም ጣልያን ሳያሰራው አይቀርም ተብሎ የተገመተ የውሃ ማስወገጃ ቦይ በግንባታው ላይ ጫና ፈጥሯል፤ ሌላው አካባቢ ግን በጥሩ ሂደት ላይ ነው ብለዋል - ኢንጂነር በኃይሉ፡፡
21 ኪሎ ሜትር በሚሆነው የፕሮጀክቱ አካል ላይ ሁሉም አይነት የግንባታ ክንውኖች እየተተገበሩ ሲሆን፤ አብዛኛው የግንባታ ስራ በ2006 ዓ.ም ይጠናቀቃል፡፡
የሃዲድ ማንጠፍ ስራዎችም በዚያው አመት ይጠናቀቃሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡ የኤሌክትሪፊኬሽን ስራዎችም በብዛት ይሰራሉ፡፡
በ2007 ዓ.ም መጨረሻ ላይ የመጀመሪያው ምዕራፍ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ስራ ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የባቡር ፕሮጀክቱ በቻይናው የባቡር መንገድ ግንባታ ድርጅት የሚከናወን ሲሆን የፕሮጀክቱ ጠቅላላ ወጪ 475 ሚ.ዶላር ነው፡

 

 

Page 12 of 17