የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ መምህራን በተማሪዎችና በአስተዳደር መካከል የነበረው ውጥረት እንዲረግብ ጥረት በማድረጋችን በኮሌጁ ቅጽር ግቢ ከሚገኙ መኖርያዎቻችን አለአገባብ ልቀቁ ተብለናል አሉ፡፡ በኮሌጁ አስተዳደር እና በተማሪዎች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት የመማር ማስተማር ሂደቱ ዘንድሮ ብቻ ሁለት ጊዜ ተቋርጦ የቆየ ሲሆን ባለፈው ሰኔ ወር መጨረሻ ተማሪዎች ባሰሙት ተቃውሞ ከመንበረ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት በተጻፈ ደብዳቤ መደበኛ ትምሕርት እስከ መስከረም 2006ዓ.ም እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡ ይሁንም እንጂ የኮሌጁ መምህራን እና ሌሎች ግለሰቦች ባደረጉት ጥረት የዘንድሮ ተመራቂ ተማሪዎች ምረቃ ባለፈው ሐምሌ 27 የተከናወነ ሲሆን መምህራኑ ልዩነት ለማጥበብ መሞከራችን የተማሪዎቹ ወገንተኛ ተደርገን በመቆጠር አላግባብ ከመኖርያ ቤታችን እንድንለቅ ተደርገናል ብለዋል፡፡
ስለ ጉዳዩ የጠየቅናቸው ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የኮሌጁ መምሕር ራሳቸውን ጨምሮ ከ5 እስከ 15 ዓመት በኮሌጁ ቅጽር ግቢ የኖሩ መምህራን እንዳሉ ገልፀው ነሀሴ 8 ተጽፎ ነሀሴ 9 ለመምህራኑ በተሰጠ ደብዳቤ ቤቶቹን በ20 ቀናት ልቀሉ ተብለናል ብለዋል፡፡
ሌላው ለአዲስ አድማስ አስተያየት የሰጡ መምሕር በበኩላቸው ቤቶቹ ለእድሳት ይፈለጋሉ ቢባልም ምትክ መኖርያ ሳይዘጋጅልን በተለይ በጾምና በክረምት ልቀቁ መባላችን አግባብነት የለውም ብለዋል፡፡
የኮሌጁን አስተዳደርም ሆነ የበላይ ጠባቂውን ብፁዕ ዶክተር አቡነ ጢሞቴዎስን ለማግኘት ያደግነው ጥረት ባይሳካም ለኮሌጁ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለመምህራኑ የቤት አበል ተሰጥቶ ግቢውን እንዲለቁ ቀደም ብሎ ብሎ የታሰበበት እንደሆነ ገልፀው በድንገት ውጡ መባላቸው አግባብነት የለውም ብለዋል፡፡

Published in ዜና

የብሉ ናይል ፊልምና ቴሌቪዥን አካዳሚ ተማሪዎች ክፍያ ተከለከልን አሉ
በብሉ ናይል ፊልምና ቴሌቪዥን አካዳሚና በስዊዘርላንዱ ቴሌ ፊልም ጂኤምቢኤች ትብብር የተሰራው “ሆራይዘን ቢዩቲፉል” የተሰኘ ፊልም ውዝግብ አስነሳ፡፡ በፊልሙ ላይ የተሳተፉ ተማሪዎች አካዳሚው የሚገባንን ክፍያ ከልክሎናል ብለዋል፡፡ ብሉ ናይል ፊልምና ቴሌቪዥን አካዳሚ በበኩሉ፤ ፊልሙ ትምህርታዊ እንጂ ለገበያ የተሰራ እንዳልሆነ ጠቁሞ፤ ወደፊት ገቢ ከተገኘበት ለፀሐፊዎች አስር በመቶ ይከፈላል ብሏል፡፡ 

የ90 ደቂቃ ርዝማኔ ያለው “ሆራይዘን ቢዩቲፉል” ፊልም በአንድ የውጪ ዜጋና በሶስት የብሉ ናይል ፊልምና ቴሌቪዥን አካዳሚ ተማሪዎች የተፃፈ ሲሆን በተፈጠረው ውዝግብ እስካሁን ለእይታ እንዳልበቃ ተማሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
“የፊልሙን ፅሁፍ ስናዘጋጅ ከሶስት ወር በላይ ወስዶብናል፤ የተከፈለን ግን ለእያንዳንዳችን 2500 ብር ብቻ ነው” ያሉት ተማሪዎቹ፤ ሥራውን ስንጀምር ትምህርታዊ ፊልም ነው ተብለን ነው፤ መጨረሻ ላይ የቴሌ ፊልም ተወካይ እስቴፈን ጃገር 14500 ዩሮ (364ሺ276 ብር ገደማ) ለተማሪዎች ክፍያ ብሎ ቢሰጥም የብሉ ናይል ትምህርት ቤት ባለቤት አቶ አብርሃም ሃይሌ ገንዘቡ ሌላ ትምህርታዊ ፊልም ይሰራበታል በማለት ከልክለውናል ብለዋል፡፡ ፊልሙን ስንፅፍ ለትራንስፖርትና ሌሎች ወጪዎችን ከኪሳችን ገንዘብ ስናወጣ ነበር ይላሉ - ተማሪዎቹ፡፡
የብሉ ናይል ፊልምና ቴሌቪዥን አካዳሚ ምክትል ስራ አስኪያጅና የአቶ አብርሀም ሀይሌ ህጋዊ ወኪል ወ/ሮ ፅጌሬዳ ታፈሰ በበኩላቸው፤ “ፊልሙ ትምህርታዊ እንጂ ለገበያ የሚቀርብ አይደለም፤ ፊልሙ እንዲሰራ የፈለግነው ተማሪዎች የእውቀት ልውውጥ እንዲያደርጉ ነው” ብለዋል፡፡ ምንአልባት በቲቪ ወይም ፕሮጀክቶች ላይ ታይቶ ገቢ ካስገኘ 10በመቶ ለፀሀፊዎች ይሰጣል፤ ለዚህ ነው ውል የተፈራረምነው ሲሉም አብራርተዋል፡፡ የስዊዘርላንዱ ቴሌ ፊልም ተወካይ ለተማሪዎቹ እንዲከፈል ሰጥቷል ስለተባለው ገንዘብ የተጠየቁት ወ/ሮ ጽጌረዳ፤ የቴሌ ፊልም ተወካይ እስቴፌን ጃገር በመሄጃው ቀን ለተማሪ ክፍያ ብሎ 14500 ዩሮ (364ሺ 276 ብር ገደማ) መስጠቱን አምነዋል፡፡
ይሁን እንጂ ት/ቤቱ ገንዘቡን ለተማሪዎቹ ከማከፋፈል ይልቅ ለሌላ ትምህርታዊ ፊልም እንዲውል በመወሰን ብሩ ባንክ ተቀምጧል ብለዋል፡፡ “ሆራይዘን ቢዩቲፉል” ከስድስት ማሊዮን ብር በላይ በሆነ በጀት በአካዳሚውና በስዊዘርላንዱ ቴሌ ፊልም ትብብር የተሰራ ፊልም ነው፡፡ በሌላ በኩል እነዚሁ ተማሪዎች ለአንድ ዓመት የተማሩበት ሰርተፊኬት አልተሰጠንም ማለታቸውን በተመለከተ ወ/ሮ ፅጌረዳ ተጠይቀው ሲመልሱ፤ “ሰርተፊኬት የተከለከሉት ያላሟሉት ነገር ቢኖር ነው፤ አልያም የስምንት ደቂቃ የመመረቂያ ፕሮጀክት አላጠናቀቁ ይሆናል፤ ይሄ እንዳይከሰት ብለን ብዙ ጊዜ ማስታወቂያ አውጥተናል፤ ለእያንዳንዱ ተማሪ ደውለናል፤ ከአሁን በኋላ ግን አመት ስላለፋቸው ፈፅሞ አናስተናግዳቸውም” ብለዋል - ወ/ሮ ፅጌረዳ ታፈሰ፡፡

Published in ዜና

ዛሬ የሚጀመረው 14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የመክፈቻ ውድድር በሆነውና የመጀመርያው የሜዳልያ ሽልማት ስነስርዓት በሚደረግበት የሴቶች ማራቶን እንዲሁም በወንዶች 10ሺ ሜትር በሚካሄደው የመጀመርያው የትራክ ፍፃሜ ውድድር፣ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ለቀጣይ ውድድሮች መነቃቂያ የሚሆኑ ድሎችን ያስመዘግባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
205 አገራትን የወከሉ ከ2500 በላይ አትሌቶች ይሳተፉበታል የተባለውንና በ200 አገራት በቀጥታ የቴሌቭዥን ስርጭት የሚተላለፈውን 14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እስከ 5 ቢሊዮን የሚደርስ ተመልካች ይከታተለዋል፡፡
ቲኪ ገላና ፤ ማራቶን ልዕልቷ
በኦሎምፒክና በዓለም ሻምፒዮና
ባለፉት ሁለት ዓመታት በተደረጉት የኦሎምፒክ፤ የዓለም ሻምፒዮና እና ትልልቅ ዓለም አቀፍ የማራቶን ውድድሮች የኢትዮጵያ እና የኬንያ ማራቶኒስቶች ውጤታማ መሆናቸው፣ በሞስኮ የሴቶች ማራቶንም የሜዳልያው ድል ከሁለቱ አገራት አትሌቶች እንደማይወጣ ከፍተኛ ግምት ያሳደረ ሆኗል፡፡ ይሄም ሆኖ በውድድሩ የሞስኮ የአየር ንብረት እስከ 30 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ይሆናል ተብሎ መጠበቁ፣ ውድድሩን ለአፍሪካውያን አትሌቶች ፈታኝ እንደሚያደርገውና ምናልባትም የራሽያ፤ የጃፓንና አሜሪካ አትሌቶች ሊያሸንፉ የሚችሉበት እድል ሊፈጠር እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡
በ29ኛው የለንደን ኦሎምፒያድ፣ በማራቶን የወርቅ ሜዳልያ የወሰደችው ቲኪ ገላና ከሁሉም ልቃ ልታሸንፍ እንደምትችል ግምት ተሰጥቷታል፡፡ ቲኪ በማራቶን የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያ ክብሯ ላይ የዓለም ሻምፒዮን ለመሆን ከቻለች፣ ይህን ድርብ ድል በመጎናጸፍ ሁለተኛዋ አትሌት ትሆናለች፡፡ በዚህ የውጤት ክብረወሰኗ የምትታወቀው በ1987 እ.ኤ.አ በማራቶን የዓለም ሻምፒዮን ከሆነች በኋላ በሲኦል ኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያ የወሰደችው ፖርቱጋላዊቷ ሮዛ ሞታ ነበረች፡፡ ከቲኪ ገላና ሌላ ይህን እድል ይዛ ሞስኮ ላይ የምትሮጠው በአቴንስ ኦሎምፒክ 2004 እ.ኤ.አ ላይ የወርቅ ሜዳልያ የወሰደችው የጃፓኗ ሚዚኩ ኒጎቺ ብትሆንም የማሸነፍ እድሏ ጠባብ ነው ተብሏል፡፡
ከ2 ዓመት በፊት በደቡብ ኮርያዋ ከተማ ዳጉ በተደረገው 13ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና፣ የኬንያ ማራቶኒስቶች ከአንድ እስከ ሶስት ተከታትለው በመግባት የበላይነት ቢይዙም፣ በዘንድሮው ውድድር ግን እምብዛም ግምት አልተሰጣቸውም፡፡ ኢትዮጵያ ባለፉት 10 ወራት ትልልቅ የማራቶን ውድድሮችን ያሸነፉ ማራቶኒስቶችን በሞስኮ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ማሳተፏ ከፍተኛ ግምት አስገኝቶላታል፡፡ የኦሎምፒክ ሻምፒዮኗ ቲኪ ገላና፤ ዘንድሮ በተካፈለችበት የለንደን ማራቶን 2 ሰዓት ከ36 ደቂቀቃ ከ55 ሰኮንዶች በማስመዝገቧ ከዓለም ሴት ማራቶኒስቶች በ2ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ በውድድር ዓመቱ የፍራንክፈርት ማራቶንን ያሸነፈችው መሰለች መልካሙ፤ ከዓለም 10ኛ ደረጃ ላይ ናት፡፡ የአምስተርዳም ማራቶንን ያሸነፈችው መሰረት ሃይሉ፤ ከዓለም 12ኛ፣ ከዓለም 13ኛ የሆነችው መሪማ መሃመድ እና የፓሪስ ማራቶንን ያሸነፈችው ፈይሴ ታደሰ በኢትዮጵያ ቡድን ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተሳትፎ ታሪኳ በማራቶን ውድድር በሁለቱም ፆታዎች ከአንድ በላይ የወርቅ ሜዳልያ አግኝታ አታውቅም፡፡ በ2001 እ.ኤ.አ ገዛኸኝ አበራ ብቸኛው የወርቅ ሜዳልያ ባለ ድል ነበር ፡፡ በሴቶች ማራቶን ኢትዮጵያ በዓለም ሻምፒዮናው ያስመዘገበችው ብቸኛው ሜዳልያ በ2009 እ.ኤ.አ አሰለፈች መርጊያ ያስመዘገበችው ነሐስ ብቻ ነው፡፡

10ሺ ሜትርና የኢትዮጵያ ያልተደፈረ ክብር ፤ የርቀቱ ንጉስ በሌለበት
በ14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና፤ በረጅም ርቀት የአትሌቲክስ ውድድር የምንግዜም ምርጥ ሯጭ የሆነው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ አለመሳተፍ ያልተጠበቀ ክስተት ሆኖ ብዙዎችን አነጋግሯል፡፡ በርካታ የአትሌቲክስ ሚዲያዎች፣ ቀነኒሳ በቀለ በ10ሺ ሜትር የኢትዮጵያ ቡድን በተጠባባቂነት በመያዙ እና በ5ሺ ሜትር ባለመመረጡ ግራ ተጋብተዋል፡፡
አትሌት ቀነኒሳ በቀለ፤ በ14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ10ሺ ሜትር በተጠባባቂነት መያዙ የመወዳደር እድሉን እንደሚያጠብበውና በሙሉ ብቃት ለመወዳዳር እንደማይችል በመረዳት ወደ ውድድሩ ላለማቅናት መወሰኑን ተናግሯል፡፡ ይህ ችግር ሊፈጠር የቻለው ለ3 ዓመታት ከዘለቀበት ጉዳቱ ሙሉ ለሙሉ ባለማገገሙ እንደሆነም ተናግሯል፡፡
በዛሬው 10ሺ ሜትር ውድድር ማን ሊያሸንፍ እንደሚችል ግምቱን የጠየቅነው ቀነኒሳ፤ በርቀቱ የሚካሄደው ውድድር በወቅታዊ ብቃት ላይ የሚወሰን እንደሆነ ገልፆ፣ ከሁሉም የትራክ ውድድሮች ለግምት የሚያስቸግረው 10ሺ ሜትር ነው ብሏል፡፡ በፈታኝነቱ በሚታወቀው በዚህ ውድድር፤ ቀነኒሳ በቀለ አለመሳተፉን ተከትሎ የወርቅ ሜዳልያው ግምት በዋናነት ለእንግሊዛዊው ሞፋራህ ተሰጥቷል፡፡ በወንዶች የ10ሺ ሜትር ቡድን ከ2 ዓመት በፊት በዴጉ የዓለም ሻምፒዮና ለኢትዮጵያ ብቸኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ያስመዘገበውና በቀጥታ ተሳታፊ የሚሆነውን ኢብራሂም ጃይላን ጨምሮ ደጀን ገብረመስቀል፣ አበራ ኩማና ኢማና መርጋ ኢትዮጵያን ይወክላሉ፡፡
ቀነኒሳ በ10ሺ ሜትር በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ አራት የወርቅ ሜዳልያዎች፤ በኦሎምፒክ 2 የወርቅ ሜዳልያዎች የወሰደ ብቸኛ አትሌት ነው፡፡ በርቀቱ የዓለም ሪከርድ እና የዓለም ሻምፒዮና ሪከርድም በእጁ ይገኛል፡፡ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ፤ በ10ሺ ሜትር የዓለም ሪከርድን ከያዘ 10 ዓመት እንዲሁም በ5ሺ ሜትር የዓለም ሪከርድን ከያዘ 7 ዓመት ሆኖታል፡፡ በሞስኮ የዓለም ሻምፒዮና ባይሳተፍም በሪከርዶቹ ሳቢያ ከሁለቱም ርቀቶች ውድደሮች ጋር ስሙ መነሳቱ እንደሚያፅናናው የሚናገረው ቀነኒሳ ይህን ታሪኩን ቢኩራራበትም ምንም ገቢ እንደማያገኝበት አብራርቷል፡፡ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ታሪክ ቀነኒሳ በቀለ፤ 6 ሜዳልያዎች (5 የወርቅ እና 1 የነሐስ) በማስመዝገብ፣ ከዓለም 6ኛ ከኢትዮጵያ 2ኛ ነው፡፡ በ2011 እ.ኤ.አ በ12ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና፤ በ10ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳልያ ሲጎናፀፍ 26 ደቂቃ ከ46.31 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ ያስመዘገበው የዓለም ሻምፒዮና ሪከርዱ ነው፡፡በ10 ሺ ሜትር ወንዶች ከ1983 እ.ኤ.አ ጀምሮ በተካሄዱ 13 የዓለም ሻምፒዮናዎች ኢትዮጵያ 9 የወርቅ ሜዳልያዎች ወስዳለች፡፡ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በዓለም ሻምፒዮና የተሳትፎ ታሪኳ፤ 9 የወርቅ፣ 4 የብርና 4 የነሐስ ሜዳልያዎችን ሰብስባለች፡፡

“የኢትዮጵያ ሥነጥበብ መነሻው ፎቶግራፍ ነው”
ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ሐምሌ 24 ቀን 2005 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሰዓሊያንና ቀራፂያን ማህበር ከሩሲያ ሳይንስና ባህል ማዕከል ጋር በመተባበር የኢትዮጵያ ሥነ ጥበብን ታሪክ ርዕስ ያደረገ የውይይት መድረክ አዘጋጅተው ነበር፡፡ በዕለቱ የማህበሩ ሊቀመንበር ሰዓሊ ስዩም አያሌው ባደረጉት ንግግር፤ በአዲስ መልክ ከተመሠረተ ሁለት ዓመት ያስቆጠረው ማህበሩ፤ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በመነጋገር ሰዓሊና ቀራፅያኑን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ ሥራዎች መሰራታቸውንና ተስፋ ሰጪ ውጤት መገኘቱን ጠቁመዋል፡፡ በማህበሩ፣ በአባላቱ ሕይወትና ሥራዎች እንዲሁም በሥነ ጥበብ ታሪክ ዙሪያ የሚወያየው ወርሃዊ መድረክ በቀጣይነት እንደሚካሄድ ሊቀመንበሩ ገልፀዋል፡፡
ወርሃዊ የውይይት ፕሮግራሙ የተጀመረበት ዕለት የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት መሥራች የሰዓሊ አለ ፈለገ ሰላም 90ኛ ዓመት የልደት በዓል የሚከበርበት ስለበር ባለታሪኩ በቦታው ባይገኙም የሙያ አጋሮቻቸው ሻማ በማብራትና ስለ ሰዓሊው የሕይወትና የሥራ ታሪክ ንግግር እንዲቀርብ በማድረግ “አንጋፎችን ማድነቅ መቻል መሰልጠን መሆኑን” አሳይተዋል፡፡
የአንጋዳው ሰዓሊ አለ ፈለገ ሰለሞን የሕይወትና የሥራ ታሪክ በወፍ በረር ቅኝት ያመለከቱት ሰዓሊ ዜና አስፋው ባለታሪኩን የገለጿቸው “ከባድ ሊባሉ የሚችሉ ብዙ ችግሮች ቢገጥሙትም ተሸንፎ ወድቆ አያውቅም” በሚል የመግቢያ ንግግር ሲሆን ለዚህም ሦስት ማሳያዎችን አቅርበዋል። የመጀመሪያው በፍቼ ከተማ የተከሰተ ነው፡፡

በልጅነታቸው ከጓደኞቻቸው ጋር የገና ጨዋታ ሲጫወቱ በተፈጠረ ግጭት የአንድ ልጅ ሕይወት ያልፋል፡፡ ልጅ አለ ፈለገ ሰላም ለእስር ይዳረጋሉ፡፡ የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው ወደ መገደያቸው ሲሄዱ “ዝም ብዬማ አልገደልም” ብለው ራሳቸውን ወደ ገደል ይወረውራሉ፡፡ በዕለቱ ሞት የተፈረደባቸው ሰዎች የራሳቸውን መቀበሪያ እየቆፈሩ ሲገደሉ አለ ፈለገሰላም ቁልቁል የተወረወሩበት ገደል ማረፊያቸው የዝንጀሮ ጉድጓድ ሆነና ሕይወታቸው ሊተርፍ ቻለ፡፡
አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ በተፈሪ መኮንንና በተግባረ ዕድ ትምህርት ቤቶች ተምረዋል፡፡ አፄ ኃይለሥላሴ ውጭ አገር ሄደው እንዲማሩ ዕድሉን ከሰጧቸው ተማሪዎች አንዱ ሆነው ደርሰው ሲመለሱ የሥነ ጥበቡ ትምህርት ቤትን በመመሥረት ለአገራቸው ታላቅ ተግባር ፈፀሙ። ይህንንም ለማሳካት ብዙ ችግሮች ገጥሟቸዋል። በሥራ ዓለም ከገጠሟቸው ችግሮች ሌላኛው በ1975 ዓ.ም የከሰተ ነው፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሊያሳትም ለፈለው ካላንደር ሰዓሊ አለ ፈለገሰላምን ያስጠራና የኢትዮጵያዊያን ሴቶች የሹሩባ አሰራርን የሚያሳዩ ስዕሎች እንዲሰሩ ያዟቸዋል፡፡ ከተሰሩት ስዕሎች አንዱን ያዩት የደርግ ባለስልጣናት እኛን ፋሽስቶች ለማለት ነው የ”ስዋስቲካ” ቅርጽ የሰጠኸው ብለው ይወነጅሏቸዋል፡፡

ከዚህም በላይ ይገደሉ የሚል መመሪያ ተሰጥቶባቸው ሳለ የሚያውቃቸው አንድሰው የተወሰነባቸው ውሳኔ ሲያይ በስዕሉ ላይ የሚታውን ዲዛይን ባህላዊነት የሚመሰክሩ ምሁራንና የሃይማኖት አባቶችን በምስክርነት በማቅረብ ሕይወታቸውን ታደገው፡፡
የሰዓሊውን ሥራና ታሪክ ያስቃኙት ሰዓሊ ዜና አስፋው ባለታሪኩ የገጠማቸው ሦስተኛ ከባድ ችግር ብለው ያቀረቡት ከመርካቶ አዲሱ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ጋር የተያያዘውን ገጠመኝ ነው። ለቤተክርስቲያኑ የጣራና የግድግዳ ስዕሎችን እንዲሰሩ ሰዓሊ አለ ፈለገሰላም ይጋበዙና ሥራውን ይጀምራሉ፡፡ በባህላዊ መንገድ ተመሳሳይ ሥራዎችን የሚሰራ አንድ ሰው ይመጣና ሰዓሊ አለ ፈለገሰላምን አብሬዎት ልሥራ ይላቸዋል፡፡ ረዳት ካስፈለገኝ እጠራሃለሁ፤ አሁን ላስፈለገኝም ይሉታል፡፡ በሰጡት መልስ ያልተደሰተው ሰው ዝቶባቸው ይሄዳል፡፡ በዚያው ሰሞን በደብረ ዘይት መንገድ ከባድ የመኪና አደጋ ገጥሟቸው በፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ከፍተኛ ሕክምና ተደርጐላቸው ሕይወታቸው ተረፈ፡፡
በመቀጠል በዕለቱ ለውይይት በተመረጠው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ለውይይት መሻ የሚሆን ንግግር እንዲያቀርቡ በዘርፉ ጥናት በመሥራት የሚታወቁት አቶ እሰየ ገብረመድህን ተጋበዙ፡፡
“የኢትዮጵያ ሥነ ጥበብ ታሪክ በጣም ሰፊና ረጅም ብቻ ሳይሆን የአገሪቱን ታሪክ ያህል ዕድሜ ያለው ነው” በማለት ገለፃቸውን የጀመሩት፡፡ አቶ እሰየ ገብረመድህን፤ የክርስትና፣ የአይሁድ፣ የእስልምናና የልዩ ልዩ እምነት ተከታዮች አሻራ በኢትዮጵያ ሥነ ጥበብ ታሪክ ላይ ቢኖርም የክርስትና ጥበብ ገዥ ሆኖ ይታያል ብለዋል፡፡ ክብ ፊት ያላቸው “መልክዓ ስዕሎች” ፣ የመስቀልና የጽላት (ታቦት) ላይ ስዕልና ጽሑፎችን በምሳሌነት አቅርበዋል፡፡
በአገራችን የሥነ ጥበቡ ታሪክ ውስጥ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ያለው የጥበብ ሥራ መስራት የተጀመረው ከ19ኛው ክፍለ ዘን በኋላ ነው ያሉት ንግግር አቅራቢ ባህላዊውን የተካው ዘመናዊ አሰራር ከዚህ ዘመን ጀምሮ መታየት መጀመሩን አመልክተዋል፡፡ የፎቶግራፍ ወደ አገራችን መግቢትም ለአዲሱ ለውጥ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓልም ብለዋል፡፡
አውሮፓዊያን “ህዳሴያችን” ከሚሉት ከ15ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የስዕል አለባዊያን የሆኑትን ጥልቀት፣ ስፋት፣ ርቀት፣ ቅርበት፣ ብርሃን፣ ጨለማ፣ መስመርን በተለከተ ዕውቀቱ ነበራቸው፡፡
ዕውቀቱን ወደዚህ ደረጃም ያሳደጉት የጥንቱን ግሪክንና የሮምን ጥበብ በማሳደግ ነው ካሉ በኋላ “እኛ ከካሜራ በፊት ይህን አልደረስንበትም፡፡ ካሜራ ወደ ዘመናዊነት እንድንገባ ረድቶናል፡፡”
ከ1920ዎቹ በኋላ ባህላዊ የሚባሉት የቤተክርስቲያን ሰዓሊያን ሳይቀሩ ሥራዎቻቸውን ለማሳደግ የጠሩትና በስዕላቸው እውነትና ውበትን ለማሳየት መሞከር የጀመሩት ከፎቶግራፍ ጋር እያነፃፀሩ መሆን የጠቆሙት ጥናት አቅራቢው ከ1920 ዓ.ም በኋላ ዘመናዊ ትምህርት ያገኙ ሰዎች ዘመናዊ የስዕል ጥበብን መማር መቻላቸው ዘናዊውንአ ሰራርን የሚተሉ ሰዓሊያንን ከማስገኙቱ ባሻገር የሥነ ጥበብ ታሪካችን መነሻ ሆኗል፡፡ ዛሬ ላይ ቆመው ነገን እያሰቡ የሚስሉ ሰዓሊያን የሚታዩትም ከዚያ በኋላ መሆኑን ገለፁ፡፡
የአውሮፓዊያን የስዕል ዕድገት ብዙ ሲያነጋግር የምንመለከተው የሥነ ጥበብ ታሪካቸውን እየተከተለ ከትላንት ወደ ዛሬ የተሻገር ጥበብ ስለሆነ ነው ያሉት አቶ እሰየ ገብረመድህን የእኛ ባህላዊ አሳሳል መገልበጥን፣ መኮረጅን፣ ያንኑ አሳምሮ ለመሥራት የመሞከር ጥረት የሚታይበት ነበር ካሉ በኋላ የእኛ ጥበብ ወዴት ያድጋል? ለሚለው ጥያቄ የሰለጠነው ዓለም የሥነ ጥበብ ታሪክ የመከተል መስመር መያዙን በማመልከት ሲያጠቃልሉ የተለያዩ አስተያየትና ጥያቄዎች ከተሰብሳቢዎች ተሰንዝረዋል፡፡
ከ1500 ዓመት በፊት የተፃፈ “ነገር ክዋክብት” በሚል መጽሐፍ ውስጥ አሳተ ነፍስ የሚሉ ኮከቦች፣ ግማሽ ሰው ግማሽ እንስሳ የመሳሰሉ ስዕሎችን ይዟል፡፡ እንዲህ ዓይነት አሳሳል በሁኑ ጊዜ ዘናዊ የሚባልና በፍልስፍና ላይ የተመሰረተ ነው ይባላል፡፡ ታዲያ ባህላዊውንና ዘመናዊውን አሳሳል እንዴት ማስታረቅ ይቻላል?
የአራችን የስዕል ጥበብ ዕድገቱ ምን ይመስላል? የስዕል ሐያሲ ሳይኖር ስለ ዕድገቱ መነጋገር ይቻላል ወይ?
ግሎባላይዜሽን በኢትዮጵያ ሥነ ጥበብ ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ ምን ይመስላል?
የኢትዮጵያ ስዕል ከየት ጀመ ለሚለውጥያቄ በሰነድ የደገፈ ማስረጃ ብዙ አናገኝም፡፡ ዛሬ በቀረበው የጥናት ወረቀት እንደተረዳሁት አሁን አየሰራንበት ያለው ዘይቤ የፎቶግራፍ ጥበብን መነሻ ያደረገ ነው መባሉ ማርኮኛል። አንድ ጥያቄ ግን አለኝ፤ ከባህላዊ ወደ ዘመናዊው አሳሳል ሽግግር ስናደርግ ምን ተጐዳን? ምንስ ተቀምን?
አቶ እሰየ ገብረመድህን ለሥነ ጥበብ ጊዜህን፣ ዕውቀትህን፣ ሃሳብህን..ሰጥተህ ብዙ ሠርተሃል። እንደዚህ ዋጋለ መክፈል እንዴትና በምን ምክንያት ፈቀድክ? በሐያሲና በርት ሂስቶሪያን መሐል ያለው አንድነትና ልዩነት ምንድነው?
በዚህ መልኩ ለቀረቡ በርካታ ጥያቄና አስተያየቶች አቶ እሰየ ገብረመድህንና ሌሎችም የስብሰባው ታዳሚዎች ምላሽና ደጋፊ ሃሳቦች አቅርበዋል፡፡ የፎቶ ግራፍ ጥበብ አገራችን ከገባ በኋላ የቤተክርስቲያን ሰዓሊያን የሚባሉት ሳይቀሩ ፎቶግራፍን አየተከተሉ ውበትና እውነትን ወደመሳል ተሸጋግረዋል ተብሏል፡፡
የ”ውበት” እና “እውነት” ምንነት አክራሪና በቀላሉ መልስ እንዳማይሰጠውና ከሰው ሰው፣ ከገር አገር፣ ከባህል ባህል…እንደሚለያይ ተነግሯል። ጥንታዊ የአገራችን ሰዓሊያን ውበትና እውነትን መርምረው ሳይሆን ተፈጥሮን የሚወክል ስዕል ይሰሩ እንደነበርም ተጠቁሟል፡፡
ከዋክብትን፣ የግማሽ ሰውና የግማሽ እንስሳ ስዕል በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ አገራት ጥንታዊ ስዕሎች ውስጥ ይታይ ነበር፡፡ እንዲህ ዓይነት ሥራዎች የተገኙት የሥነ ጥበብ ታሪክን ማዕከል አድርገው ሳይሆን በፈ ታሪክ ላይ ተመስርቶ ነው፡፡ በግሪክ ሰውና እንስሳ ተቀላቅለው የሳለ ሥራ አለ፡፡ የቻይናዎች ድራጐንም ተመሳሳይ ታሪክ ያለው ነው፡፡
የእስራኤሉ ንጉሥ ሰለሞን ወደ ገነት ለመሄድ ፈልጐ ፈረስና አሞራን አዳቅሎ ባገኘው ልዩ ፍጡር እንስሳ ዓላማውን ማሳካቱና ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያዊቷ ንግስተ ሳባ የተጠቀመችበት ነገር አለ ተብሎ የሚነገረው አፈ ታሪክ ሌላው ማሳያ ነው፡፡ አፈ ታሪክ ሱሪያሊዝም አይደለም፤ ሱሪያሊዝምም አፈ ታሪክ አይደለም፡፡ “ኢዝም” ሲመጣ ግን ንቅናቄን ያመለክታል ተብሏል፡፡
የሥነ ጥበብ ታሪክና ዕውቀቱ ባይኖራቸውም አስገራሚ የስዕሉ ሥራዎችን መስራት የቻሉ ሕዝቦች በተለያዩ ቦታዎች ይገኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ ጥንታዊ የባህል ስዕሎችም በዚህ ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ፡፡
ፎቶግራፍን መነሻ የሚያደርገው የአገራችን የስነ ጥበብ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ሊባል የሚችል ዕድገት ተመዝግቧል፡፡ ለዚህም እንደማሳያ ስዕልና ቅርፃ ቅርጽ ሕብረተሰቡን እያገለገለ መሆኑን ተነግሯል፡፡ ይህም በግሎባላይዜሽን ተጽእኖ የተገኘ ውጤት ነውም የሚል ሃሳብ ቀርቧል፡፡
ሰዓሊያን ዘመናዊውን የአሳሳል መንገድ መከተል ሲጀምሩ ከባህላዊው የወሰዱት ነገር አለመኖሩ ጉዳት ነው። በዚየ አጋጣሚ ኢትዮጵያዊያን ዓለም አቀፉን የአሰራር ዘዴ መከተላቸው ዕድገት እንደሆነም ተገልጿል፡፡
የስነ ጥበብ ታሪክ አጥኚ ሙያው ውስጥ ያለና የጥበቡን ባህላዊና ዘመናዊ ታሪክ የሚያጠና ባለሙያ ሲሆን ሐያሲው የግድ ሙያው ውስጥ መገኘት እንደሌለበትና ጋዜጠኞች የስዕል ሐያሲ ሆነው ሲሰሩ የሚታይና የሚመረጥም መሆኑ ተገልፆ የዕለቱ ስብሰባ ተጠናቋል፡፡

 

Published in ጥበብ

                    ባለፈው ሳምንት “በስብሃት ላይ የተቃጣው የሚካኤል ዱልዱም ሰይፍ” በሚል ርዕስ አስተያየት የፃፈው ሚልኪ ባሻ ጥሩ ወዳጄ ነው፡፡ በባህርዩም ዝምና ዝግ ያለ አመለ ሸጋ ነው፡፡ በአለፍ ገደም ስንገናኝ ስለ ክርስትና እምነታችን፣ ስለ መፃሕፍትና ፀሐፍቶቻቸው እናወራለን፡፡ የሚልኪ አንዳንድ የነገር ምልከታዎች ግር ቢለኝም ቀናነቱን አስቤ፣ የገባኝን ወስጄ ያልገባኝን እተዋለሁ፡፡ ሚልኪን እንደ አንባቢና “ግራ አጋቢ” ብቻ ሣይሆን በእግዚአብሔር ላይ ጽኑ እምነት እንዳለው ሰው ስለምቆጥርም መንፈሳዊ ወንድምነቱን እቀበላለሁ፡፡ ወደፊትም ይህንኑ በማድረግ እቀጥላለሁ፡፡
ነገሩን የተለየ ምሥጢር ላለማድረግ ያህል ግን እኔና ሚልኪን የማያግባቡን ሁለት አበይት ጉዳዮች የሚከተሉት ናቸው፡፡ አንደኛ ሚልኪ “ስለ እግዚአብሔር ያለን ውስጣዊ መረዳት ዓለም የማይገነዘበው፣ ምክንያት የማይገልጠው ስለሆነ በአላማኞች የሚቃጣብንን ዘለፋና የአመክንዮ ጥያቄ በዝምታ ማለፍ እንጂ ስለ እምነታችን ምሥጢር ምክንያት (Reason) ለማቅረብ ጨርሶ መነሳት የለብንም” በሚለው አቋሙ የምስማማው በከፊል በመሆኑ በዚያ ላይ ብዙ ጊዜ ተከራክረን እናውቃለን።
ሁለተኛ ሚልኪ ነገርን ባላመነው ሰው ጫማ ውስጥ ሆኖ ለመመልከት ያለውን ፍላጐት ባከብርለትም ሰውዬውና ሴትዮይቱ የራሳቸውን ጫማ አውልቀው ለእግዚአብሔር “እነሆኝ ተሸንፊያለሁ” የሚሉበትን መንገድ ከማደላደል ይልቅ ሰዎቹ በዚያው መንገዳቸው እንዲገፉበት ዕድል የሚሰጥ፣ በር የሚከፍት በመሆኑ በዚያ ግርም፣ ቅርም ሲለኝ ቆይቻለሁ፡፡
በቅርቡ ተገናኝተን ደራሲና ጋዜጠኛ አለማየሁ ገላጋይ “መልክአ ስብሃት ገ/እግዚአብሔር” በሚል ርዕስ ስላሳተመው መጽሐፍ ከሚልኪ ጋር ስናወራ፤ ሳለ በመጽሐፉ ውስጥ ከቀረቡት ጽሑፎች በአንደኛው ላይ ለአዲስ አድማስ አስተያየት ስለመፃፉ ጫፍ ጫፉን በነገረኝ ጊዜም “በመልክአ ስብሃት” ውስጥ ከተፃፉትና በአመዛኙ ተመሳሳይ ዜማ ካላቸው “ውዳሴ ስብሃቶች” መካከል ስለምን የተለየ ሚዛንና ምልከታ ባለው ሚካኤል ሽፈራው ጽሑፍ ላይ የብዕር ቀስቱን ለመስበቅ ቃጣ የሚል ግርታ የተፈጠረብኝ ወዲያው ነው፡፡ ጽሑፉ በጋዜጣ ታትሞ ባነበብኩት ጊዜ ደግሞ ያንኑ ስብሃትን “ከሌላ ማዕዘን” ያሳየንን የሚካኤል ሽፈራው ጽሑፍ በዜሮ ለማባዛት “ተጣደፍኩ” የሚል ቃል ማስፈሩን ተመልክታ፣ ከልጁ ጭምትነት ጋር የሚሄድ ስላልመሰለኝ “የመጨረሻ” ገረመኝ፡፡
እኔ ደግሞ አቶ ሚካኤል ሽፈራው፤ በቅርበት ያየውን የጋሼ ስብሃት “ስንፍና” ማንንም ሳይፈራ ግልጥልጥ ማድረጉን ሊኖረው ከሚችለው ማህበራዊ ፋይዳ አንፃር ወድጄው ስለነበር ወዳጄ ሚልኪ ባሻ፣ ጋሼ ስብሃት በህይወት ኖሮ እንኳ ቢሆን ሊያስተባብለው የማይችለውን ስንፍና ሊያስተባብልለት በመነሳቱ ደግሜ፣ ደግሜ ተገረምኩ፡፡ ክርክሩ ከየትኛው የህይወት ፍልስፍናው እንደመነጨ ለማሰብም ብዙ ጊዜ ፈጅብኝ፡፡ ብዙ ጊዜ በዚህ ጋዜጣ ላይ እምነቱን የሚነካ ጉዳይ ሲፃፍ፣ “ጌታዬ” ብሎ የሚያምነው ባላዋቂዎች ብዕር ሲብጠለጠል “ዝምታ ነው መልሴ” ያለው ሰው፤ የጋሼ ስብሃትን “ስንፍና” ከቶም ስንፍና እንዳልነበር ለማስረዳት “መጣደፉም” ወዳጄን ምን ነካው አሰኘኝ፡፡
ሚልኪ ጋሼ ስብሃት “ሰነፍ” የተባለበት ምክንያት ጠፍቶትም ባይሆን፣ ስንፍናው መገለጡ ከንክኖታልና “ስብሃትን የመሰለ የዓለምን ሥልጣኔ የለወጡ ታላላቅ መጽሐፍትን በመመርመር ዘመኑን ያሳለፈ፣ በርከት ያሉ ልቦለዶችን የፃፈ፣ እንዲሁም ቁጥራቸው የማይታወቅ የጋዜጣና የመጽሔት ጽሑፎችን ይጽፍ የነበረ ሰው… እንዴት በስንፍናና በዲሲፕሊን ማጣት ሊታማ ይችላል?” ብሎም ይጠይቃል፡፡ አዎን ጥያቄው ተገቢ ሊሆን ይችላል። መልሱ ግን በጣም ቀላል ነበር፡፡ ጋሼ ስብሃት የቱንም ያህል ያነበበ፣ የቱንም ያህል በዓለም ያለውን ዕውቀት የሰበሰበ ቢሆን በእግዚአብሔርና በሰው ዘንድ ትልቅ ግምት ለሚሰጠው ግብረገባዊ ህይወት ቁብ አልነበረውምና ያ “ሰነፍ” ያሰኘዋል፡፡
ከሁሉም የከፋው ችግር ግን የጋሼ ስብሃት ስንፍና በራሱ ተወስኖ አለመቅረቱ ነው፡፡ አቶ ሚካኤል “በመልክአ ስብሃት” መጽሐፍ ሊያሣየን እንደሞከረውም ያለ ማህበራዊና ቤተሰባዊ ኃላፊነት በዝሙትና በአልኮል ተነክሮ ለመኖር የነበረው ምርጫ ሌሎችንም ወደዚህ የአኗኗር ዘይቤ መርቷልና፣ ስንፍናውን ወደ ብዙዎች አጋብቷልና፣ ጋሼ ስብሃት የቱንም ያህል በክህሎት የታጨቀ ሰው ቢሆን ከወቀሳ የሚተርፍበት ምንም ዓይነት መከራከሪያ ሊቀርብ አይችልም፡፡
ጋሼ ስብሃት ዕድሜውን ሙሉ ለአካላዊ ሃሴቱና፣ ለዓዕምሯዊ ደስታው ሲታትር የኖረ እንጂ ለምንም እና ለማንም ኃላፊነት የሚሰማው ሰው አለመሆኑም አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው፡፡ እንኳን ለባዳው ለገዛ ቤተሰቡም ህይወት የሚጠነቀቅ አባት እንዳልነበርም ያሳለፈው ታሪክ ምስክር ነው፡፡
ለዚህ ጥቂት ማሣያ ቢሆን የሌላውን ቤቱ እንዲቆጥረው ትቼ፣ የገዛ ልጁን የመራበትን አደገኛ መንገድ ልጥቀስ፡፡ ዛሬ በህይወት የሌለች የጋሼ ስብሃት ሴት ልጅ ባል የሚስቱን ወጣ፣ ወጣ ማለት ማብዛት፣ አምሽቶ መግባትና በወጡበት ማደር መክሮ ያስቆምለት ዘንድ ሌሎች “ሽማግሌዎችን” ይዞ አቤቱታውን ባቀረበ ጊዜ፣ የጋሼ ስብሃት ምላሽ ዘግናኝ ነበር፡፡ “አንተ ምን አስጨነቀህ አያልቅ” የሚል፡፡
ሚልኪ ባሻ ግን ስለ ጋሼ ስብሃት ከሚሞግተው ሙግት አንደኛው ለወዳቂዎቹ ውድቀት ተጠያቂዎቹ ራሳቸው ግለሰቦቹ እንጂ ስብሃት አይደለም፣ ግለሰቦቹ በገዛ ምርጫቸው ያመጡት ስለሆነ ኪሣራዎችን ሁሉ በስብሃት ላይ መደፍደፍ ተገቢ አይደለም የሚል ነው፡፡ ግን ካለው ፍጥረት ጀምሮ ሳቾች የሚስቱት፣ ቀኚዎችም የሚቀኑት በጥቂት አሳቾችና በጥቂት አቅኚዎች መሆኑን ማንም አያጣውም፡፡ ቤተሰባዊ ኃላፊነትን በተመለከተም የልጆች አስተዳደግ በኋላ የህይወት ዘመናቸው ላይ የሚያመጣውን በጐና ክፉ ጐን ለመረዳት የሥነ ልቦና ሊቅ መሆን አይጠይቅም።
ሚልኪ የጋሼ ስብሃትን መረን የወጡ ሥነ ጽሑፎችም በራሱ ተሞክሮዎች የተሞሉ ፀያፍ ወሲባዊ ልምምዶች ከመሆናቸው ይልቅ በዘርፉ ባለሙያዎች ብያኔ “ሱሪያሊዝም” እና “ፋንታሲ” በሚባለው የአፃፃፍ ዘይቤ ተመድበው የሚተነተኑ የጥበብ ትሩፋቶች እንደሆኑ ሊሰብከን መቃጣቱም ሌላው የግርምቴ ምክንያት ነው፡፡
በግሌ ከሥነ - ጽሑፍ ዘውጐቹ ጋር ጠብ የለኝም፤ ግና የሚልኪ አናሎጂ የጋሼ ስብሃትን ነውሮች ለማጽደቅ የቀረበ ስለመሰለኝ በፍፁም አልተመቸኝም፡፡ ሚልኩ አውቆም ይሁን ሳያውቅ ጋሽ ስብሃት ከማህበረሰቡ ጋር ለነበረው ቅራኔና ግጭትም አድናቂ ይመስላል፡፡ “ስብሃት በባህል፣ በሃይማኖት እና በልማድ ሰንሰለት ተተብትቦ” (ይህ የሚልኪ አባባል ነው) ከነበረው ማህበረሰብ ጋር የፈጠረውን ያፈጠጠ ግጭትና ተቃርኖ የገለፀበት መንገድ ሳይንሳዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ሃይማኖታዊ ወይም ፍልስፍናዊ ከመሆኑ ይልቅ ሥነ - ውበታዊ (Aesthetical) እና ህልውናዊ (Existential) መሆኑንም የሚያገናኘው ከአለቃ ገብረሃና ጋር ነው።
“ከአለቃ ገብረሃና በመቀጠል ከማህበረሰቡ ጋር በፈጠረው ከፍተኛ ግጭትና ቅራኔ በጥሩም በመጥፎም ዝነኛ የሆነ ሰው ስብሃት ብቻ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም” የሚለን ሚልኪ፤ የጋሼ ስብሃት ጥሩው እንጂ መጥፎው እንዲነገር ፈጽሞ ፈቃደኛ አይመስልም፡፡ አለቃ ገብረሃናም ሆኑ ጋሼ ስብሃት ሰውንም አምላክንም ባለመፍራት ተመሳሳይ በመሆናቸው እኔም እስማማለሁ፡፡ አለቃ በዘመናቸው የቅኔ ሊቅ ብቻ ሳይሆኑ ሰው ሁሉ “ይሰድበኛል” ብሎ የሚፈራቸው፣ “ያንጓጥጡኛል” ብሎ የሚሳቀቅባቸው፣ የሰውን ስብዕና በመንካት የታወቁ ጋጠወጥ እንደነበሩም ታሪካቸውን አንብቤያለሁ፡፡ ይህንንም ያወቅሁት ችሎታቸው ብቻ ሳይሆን ድካማቸው ተጽፎ ስላገኘሁ ነው፡፡
የአለቃ ገብረሃናን ቅኔ አዋቂነትና የቀልድ ችሎታ አድንቆ የፃፈልን አረፈዓይኔ ሐጐስ “አለቃ ገብረሃና እና አስቂኝ ቀልዶቻቸው” በሚለው መጽሐፉ፤ ስለ ቅኔ ሊቅነታቸውና ስለ ቀልድ አዋቂነታቸው ብቻ ሣይሆን ሰውን በመዝለፍና በማንጓጠጥ፣ ከሚስታቸው ሌላ በመወስለት የታወቁ መሆናቸውንም ታሪካቸው ስለሆነ አልሸሸገላቸውም፡፡ አለቃን ከዚህ ለይቶ ማውራት ጨርሶ የሚቻል ስላልሆነም ከትርክቱ በአንደኛው ምዕራፍ ላይ “አለቃን የዝሙት መንፈስ ተጠናውቷቸው ብዙ ጊዜያቸውን በውስልትና ቢያሣልፉም እኩይ ተግባር ተሰውሮ አይኖርምና መጥፎ ግብራቸው በመጨረሻ ተገለጠባቸው” ይለናል፡፡ ጋሼ ስብሃትና አለቃ ገብረሃና ይመሳስላሉ ከተባለም ዋናው የተመሳስሎ ማሳያ የጋሽ ስብሃትን አፈንጋጭነት በኪነጥበባዊ ክህሎቱ የሚሸፍኑት ብዙ ልሂቃን ማግኘቱ ሲሆን አለቃም መጥፎ ግብራቸው በሰዎች ዘንድ የታወቀ ሆኖ ሳለ፣ በህይወት ዘመናቸው ማብቂያ ላይ እርሳቸው ራሳቸው በተግባራቸው ተፀጽተው አይነ እግራቸውን እስከለሰለሰበት ጊዜ ድረስ በነገሥታትና መኳንንቶች ቤት የሚፈለጉ ኮሜዲያን ሆነው መኖራቸው ነው፡፡ እኔ ደግሞ በሌላም ጉዳይ ተመሳስለው ቢሆን ብዬ ተመኝቻለሁ፡፡ በሚከተለው ታሪክ ምክንያት -
“አለቃ ገብረሃና ወደመጨረሻ ዘመናቸው ዝምተኛና አኩራፊ ሆኑ” የሚለን አረፈዐይኔ ሀጐስ፤ የአለቃ አንደበት አለመጠን መለጐም ያሳሰባቸው ቤተሰቦቻቸው ጋኔን ሰፍሮባቸዋል ብለው በመጠርጠር ፀበል እስኪያስጠምቋቸው ቢደርሱም አለቃ ግን “እግዚአብሔርን ላመስግንበትና ልሰብክበት፣ ቁም ነገር ልናገርበት በሰጠኝ አንደበቴ ዋዛ ፈዛዛ ስናገርበት ኖሬያለሁ” በማለት አንደበታቸውን ከልክለው፣ ከመጠጥና ጥሩ ምግብ ተቆጥበው፣ መሬት እየተኙ መኖር እንደጀመሩ ይነግረናል፡፡
ይህም ብቻ ሳይሆን አለቃ ገብረሃና አጋቶን የሚባለውንና ክፉ እንዳይናገር ድንጋይ በአፉ ጐርሶ ይኖር የነበረውን መነኩሴ ህይወት ለመኖር ይጥሩ እንደነበር፣ መፃሕፍቱንም ሰብስበው “መሳቂያና መዘባበቻ አደረግኋችሁ” እያሉ ይቅርታ ይጠይቁ እንደነበር ይተርክልናል፡፡ እናስ ማን ያውቃል ዛሬ ስለ ጋሼ ስብሃት “ልዩ ማንነት” ከሚነግሩን ብዙ ድምፆች በተለየ ጋሼ ስብሃት በዘመኑ ማብቂያ፣ በህመም አልጋ ላይ በሞት ፍርሃት እየራደ ሳለ፣ ለፈጣሪው ምን ብሎ ተናግሮ፣ ምን እንደሆነ ማን ያውቃል? ወንድሜ ሚልኪ ባሻ ግና በጋሼ ስብሃት ፍፃሜ አካባቢ አልጋው አጠገብ የተቀመጠ “ዕድለኛ” ሰው ቢሆን፣ ይህንን የፀፀት ድምጽ ለመስማት የሚናፍቅ አይመስልም፡፡ ሚልኩ፤ ጋሼ ስብሃት የኢየሱስ አድናቂ፣ የቡድሃ አወዳሽ እንጂ ውስጡ ጽድቅና ኩነኔ እንደሌለ የሚቆጥር እምነተ ቢስ ስለመሆኑ በግጥም ያረጋገጠልን ቢሆንም እንደ አማኝ ጽድቅና ኩነኔ መኖሩን ጠቅሶ በእምነት መዳን እንዳለ የሚናገርበትን ጊዜውን በውዳሴ ያባክነው ነበር፡፡ ይገርማል! ለሚልኪ ጋሼ ስብሃት ያጠፋው ምንም ጥፋት የለም፡፡ ስለዚያም የነገረን ነገር የለም፤ በእርግጥ ለማለት ያህል ብቻ ከሀተታው ጋር ጨርሶ በማይገጥም መልኩ በጽሑፉ መግቢያ ላይ “ሙሉ በሙሉም ባይሆን ከፀሐፊው ጋር የምጋራው ሃሳብ አለ፣ የፀሐፊውን ልበ ሙሉነትና ተጋፋጭነትም አደንቃለሁ፣ በየጋዜጣውና በየመጽሔቱ ስለ ስብሃት አንድ ዓይነት መወድስ በምንሰማበት ወቅት ያለ አንዳች ፍርሃት እና ማመንታት የሚሰማቸውን እና የሚያሰቡትን የገለጡበት ሁኔታ ያስቀናል” ሲል ሚካኤል ሽፈራውን ካሞጋገሠ በኋላ፣ መልሶ ደግሞ “ብዕር እንዳነሳ ያጣደፈኝ እኒህ ቢሆኑም የጽሑፌ ዓላማ ግን ወዲህ ነው” ብሎ እርሱም ያንኑ ክሊሼ (የተሰለቸ) ውዳሴ ስብሃት ደግሟል። “ተጣደፍኩ” ያለበት ምክንያትም ከዝርዝሩ ጋር ጨርሶ ይቃረናል።
እኔ ደግሞ “በመልክአ ስብሃት” መጽሐፍ ያነበብኩትን የአቶ ሚካኤል ሽፈራውን “ሌላ ማዕዘን” በጣም ወድጄዋለሁ፡፡ ሚካኤል በጋሼ ስብሃት ላይ በጣም እንደጨከነበት ቢሰማኝም ለምን እንደዚያ እንደጨከነም ይገባኛል፡፡ ከትዝብቶቹም ብዙዎቹን እጋራቸዋለሁ፡፡ እኔም ብሆን የመልክአ ስብሃት አዘጋጅ አለማየሁ ገላጋይ ከጋሼ ስብሃት ጋር የነበረኝን የቀደመ ማህበረተኝነት ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ በዚህ ሥራ ውስጥ ተሣታፊ እንድሆን ያቀረበልኝን ግብዣ ተቀብዬ ቢሆን ኖሮ ከአቀራረቡ በቀር ሚካኤል ካለው የተለየ ነገር አልልም ነበር፡፡
እኔም አንድ ዘመን ላይ በጋሼ ስብሃት እግር ሥር ቁጭ ብዬ ወሬዎቹን ያደመጥኩ፣ ትርክቶቹን ያጣጣምኩ፣ በአዋቂነቱ የተመሰጥኩ፣ እርሱ የሆነውን ለመሆን፣ ያየውን ለማየት በምኞት የናወዝኩ፣ አቅሌን ልስት፣ ወፈፍ ሊያደርገኝ አንድ ሃሙስ ሲቀረኝ፣ ከዚህ ምድር ያልሆነ ሌላ ጉሩ፣ ሌላ ረባይ (መምህር) አግኝቶ ባያረጋጋኝ፣ ሌላ የደስታ መንገድ፣ ሌላ የሃሴት ምንጭ እንዳለ አሳይቶ ባያሳርፈኝ ኖሮ እመኑኝ ጨርቄን እጥል ነበር፡፡ ይህም ሆኖ ጋሼ ስብሃት በሞተ ሰሞን ውስጤ ተሰንቅሮ በቀረ አንዳች ራሮት ምክንያት እኔ “ይለፈኝ” ያልኩትን ዕድል ሚካኤል ተጠቅሞበት በሠራው ሥራ እጅግ ተደስቻለሁ፡፡ እንደ አዝማሪ ውዳሴ ከቀረቡት ብዙዎቹ ጽሑፎች ይልቅ ሚዛን ደፍቶ ያገኘሁትም የሱን ነው፡፡ ሚልኪ ይህንን ጽሑፍ “በዶለዶመ ሰይፍ” ቢመስለውም እኔ ግን በአንዳች ተዓምር ከስለቱ በላይ የደደረ አካል ኖሮ ካልሆነ በቀር፣ ተፈጥሯዊ ሥጋና ነፍስን ዘልቃ ለመግባት የሚካኤል ሰይፍ በሁለት በኩል የተሳለች ሆና አግኝቻታለሁ፡፡

Published in ጥበብ
Saturday, 10 August 2013 12:10

ሚሊየነሩ መቃብር ቆፋሪ

የጉልማ መላኩ ሕይወትን የሚቀይር ተአምር የተፈጠረው እንደ ልማዱ በማለዳ ተነስቶ ወደ ሥራው እየሄደ ሳለ ነበር፡፡ ተአምሩ በተከሰተበት ዕለት ባለቤቱ ጐጄ፣ ከውድቅት ጀምሮ እስከ ንጋት ድረስ በመነዝነዝ፣ እንቅልፍ በዓይኑ ሳይኳል እንዲያድር አድርጋው ነበር፡፡ ከንዝንዟ ለመሸሽ በጠዋት ተነስቶ ወደ ሥራው ሲሄድ ነው ተአምሩ ያጋጠመው፡፡ የሚስቱ ጭቅጭቅ በውኃ ቀጠነ ተልካሻ ምክንያት ተጀምሮ፣ ወደ ኑሯቸው የሚመጣ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡
“ከጓደኞቼ በታች አደረከኝ፡፡ አንተ ስለመሻሻል አስበህ አታውቅ፡፡ ሲፈጥርህ ጅል አድርጐ ነው፡፡ ይኸው መቃብር ቆፋሪ ሆነህ ስንት ዓመት? 28 ዓመት ሙሉ ከመቃብር ቆፋሪነት ሳትሻሻል---- ውይይይይይ” ጐጄ ታማርራለች፣ እንደማልቀስ ይቃጣታል፡፡
“29 ዓመቴ ነው ሟቾችን በማሳረፍ ሙያ ላይ ከተሰማራሁ” ይላታል እያረማት፡፡ ጉልማ ራሱን የመቃብር ቆፋሪ ብሎ አይጠራም፤ “ሟቾችን የማሳረፍ ሥራ” ብሎ ነው ሙያውን የሚገልፀው፡፡ በሙያው ላይ ካሳለፈው ጊዜ ቅንጣት እንዲቀነስበት አይፈልግም፡፡ ጐጄ በሰጣት እርምት ብው ብላ ትጨሳለች!!
“ቁም ነገር ሆኖ ነው አፍህን ሞልተህ 29 ዓመት የምትለው? ኢንጂነር የሆንክ መሰለህ? ወይስ ማዕድን ቆፋሪ ? የሬሳ መቀበሪያ እየቆፈርክ እኔንም ሬሳ አድርገኸኝ ኖርክ፡፡ እንደው የአባቴ አምላክ ይድፋህ---ጅል ጅላንፎ!” የእርግማኗን ዶፍ ታወርድበታለች፡፡
ጉልማ ግን አይናገራትም፡፡ ዝም ይላል፡፡ ዝምታው ይብስ ያናድዳታል፡፡ ሚስቱ ብቻ ሳትሆን የመንደሩ ሰው ሁሉ ነው በጅልነቱ የሚዘባበተው፡፡ የጉልማ ጅልነት ሀገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው፡፡
“አይ ጉልማ ጅል እኮ ነህ” ሲሉት ሳቅ ብሎ ከመሄድ ባለፈ ቅርታ አይገባውም፡፡ በሕይወቱ ደስተኛ ነው፡፡ ሁሉን ነገር ይወዳል፡፡ በመቃብር ቁፋሮ ሥራው፣ በሚስቱን መነጫነጭ፣ በጐረቤቶቹን ንቀት ወዘተ--- በሁሉም ነገር ደስተኛ ነው፡፡ ያቺ ሕይወት ለሱ እንደተጣፈች ያምናል፡፡ የሚስቱን ጭቅጭቅ እንደ ሕይወቱ ሙዚቃ ነው የሚቆጥረው፡፡ ለማማረር ጊዜ የለውም፡፡
“እኔኮ እንደሌላው ወንድ ቢሰድበኝ፣ ቢመታኝ በማን ዕድሌ?” ትላለች፣ባለቤቱ ጐጄ ዝምታው ሊያሳብዳት ሲደርስ፡፡
ጠጅ የጠጣ ቀን ብቻ ረጋ ብሎ የመቃብር ቆፋሪነትን (በሱ አጠራር ሟቾችን የማሳረፍ ሙያ) ክብር ሊያስረዳት ይሞክራል፡፡ “አየሽ ጐጄ፤ በምድር ላይ መቃብር የመቆፈርን ያህል የተከበረ ሙያ የለም፡፡ የሰው ልጆች ሁሉ የኛ ደንበኞች ናቸው፤ እስቲ ምድር ላይ ካለ ሰው ወደኛ የማይመጣ ጥሪልኝ”
ከባድ ጥያቄ እንደጠየቃት በማመን ያፈጥባታል፡፡
“ደሞ ሙያ ይልልኛል ---- ምን የረባ ሙያ ሆኖ ነው?” መልስ ሲመልስላት ደስ ስለሚላት ረጋ ትላለች፡፡
“ብዙ ሙያ ብዙ ጥበብ አለው እንጂ---- እይው መጀመሪያ አፈር መምረጥ አለብሽ፤ ካህናት የሚቀበሩበት አፈር ልል መሆን አለበት፤ ይኼ ደለል እንዳመጣው ዓይነት፤ ጀግና የሆነ እንደሆን መረሬ አፈር መምረጥ አለብሽ…ምንም ያላገባች ሴት ከሆነች ደግሞ በዛፍ መካከል፤ ሀብታም የሆነ እንደሆነ ደግሞ ለምለም ሳር ያለው ቦታ ላይ ነው መቀበሪያው፡፡ መቃብሩ ሲቆፈር ደግሞ እንደው ዝም ብሎ መሬቱን ድርምስ እያደረጉ አይደለም፤ ከላይ እንደ እርከን እያደረግሽ በየደረጃው ትወርጅና እያጠበብሽ እያጠበብሽ…” ጉልማ ማስረዳቱን ይቀጥላል፡፡ ባለቤቱ ጐጄ የተናገረ ቀን ጭቅጭቋ ይቀንሳል፡፡ ክፋቱ ግን ጉልማ ብዙ የመናገር ፍላጐት የለውም፡፡ ዝምታው የሕይወቱ ዋሻ ነው፤ ራሱን የሚደብቅበት፡፡ ዝምታውን ተከትላ ጐጄ ቤቱን ስታምሰው ታመሻለች፡፡
የጐጄን ንዝነዛ ለማምለጥ በጠዋት በወጣበት ማለዳ ነበር ተአምሩ ያጋጠመው፡፡ ጐጄን ምንም ሳይናግራት ወደ መቃብር ቁፋሮ ሥራው እየሄደ ሳለ፤ ከቤተክርስትያኑ መግቢያ ላይ ሊደርስ ትንሽ ሲቀረው፤ ከቀጭኗ አስፋልት ዳር ላይ አንድ የሆነ ሻንጣ የመሰለ ነገር ያየ መሰለው፡፡ መጀመሪያ የወደቀውን ሻንጣ እንዳላየ ሆኖ ሊያልፈው ነበር፡፡ አንዳች የማያውቀው ውስጣዊ ስሜቱ ግን እግሮቹን አስሮ እንዳይንቀሳቀስ አደረገው፡፡ በቆመበት አፍታ ከራሱ ጋ ትንሽ ተሟገተ፡፡
“ምን ሊሆን ይችላል?” የሚል ዓይን ያወጣ ጉጉት በአንድ በኩል፤ “አንድ ሰው ጥሎት ይሆናል፡፡ አንስቼ ለፖሊስ ባስረክበው” የሚል ትሁት ጉጉት በሌላ በኩል ገፋፉት፡፡
ሻንጣውን በማንሳት ወስኖ የቀጭኗን አስፋልት ግራና ቀኝ ቃኘ፡፡ የሰው ዘር አይታይም፡፡ ሻንጣውን ቀስ ብሎ አነሳው፡፡ ከበድ ያለ ነበር፡፡ “ምን ቢኖርበት ነው እንዲህ የከበደው” እያለ የመቃብር ቁፋሮ ወደሚሠራበት ቤተክርስቲያን መጣደፍ ጀመረ፡፡ ትንሽ እንደሄደ ሦስት ቱታ የለበሱ ወጣቶች ከፊት ለፊቱ እየሮጡ ሲመጡ አያቸው፡፡ አንዳች ቦታ ሊደበቅ ቢፈልግም ከመደበቁ በፊት ወጣቶቹ በሶምሶማ ዱብ ዱብ እያሉ አልፈውት ቁልቁል ሄዱ፡፡ በእፎይታ ተንፍሶ ወደ ደጀ ሰላሙ ገባ፡፡
በቤተክርስትያኑ ውስጥ የተወሰኑ ምዕመናን የቅዳሴ መግቢያ ሰዓት እንዳያልፍባቸው ወደ መቅደሱ ይቻኮላሉ፡፡ ሻንጣውን እንደያዘ ከቤተክርስትያኑ ጀርባ ወዳለው መቃብር ሥፍራ እየተጣደፈ ሄደ፡፡ የመቃብር ቦታው ጭር ብሏል፡፡ የመቃብር ሥፍራው ፀጥታ ሁሌም ይማርከዋል፡፡ በሀውልቶቹ ላይ እየተረማመደ ወዲያና ወዲህ ሲል ፍፁም ሀሴት ያደርጋል፡፡
ዓለምን ሲያንቀጠቅጡ የነበሩ ሰዎች በሙሉ በእግሩ ሥር ናቸው፣ እሱ ብቻ ነው ሕያው፤ እሱ ብቻ ነው የማለዳዋን ፀሐይ መምጣት በናፍቆት መጠበቅ የሚችለው፡፡ የመቃብር ቦታው ፍቅር አጥንቱ ድረስ ዘልቆ ገብቷል፡፡ አሁን ግን ቀልቡ ሁሉ ሻንጣው ላይ ነው፡፡ የወትሮ ልማዱን ትቶ ሻንጣውን ለመክፈት ቦታ መምረጥ ጀመረ፡፡ “ሻንጣው ውስጥ ምን ይሆን ያለው” የሚለው የጉጉት ስሜቱ አእምሮውን ሊያፈነዳው ሲደርስ ወደ አንደኛው መቃብር ቤት ተንደርድሮ ገባ፡፡ መቃብር ቤቱን ከውስጥ ዘጋው እና ሻንጣውን ከፈተው፡፡ ሻንጣው ውስጥ ያለውን ነገር ሲያይ ሳይታወቀው ኡኡታውን ለቀቀው፡፡ ትንሽ ቆይቶ አእምሮውን የሚስት ሁሉ መሰለው፡፡ ሻንጣውን ዘግቶ በድጋሚ ከፈተው፡፡ ዓይኑን ማመን አልቻለም፡፡ ሻንጣው በአዳዲስ የኢትዮጵያ ብር እና የአሜሪካ ዶላሮች የተሞላ ነበር፡፡ ጉልማ ሰውነቱ ተንቀጠቀጠ፣ አፉ ደረቀበት፡፡ የሚይዝ የሚጨብጠውን አጣ፡፡ በሕልም እና በእውን መካከል የሚቃዥ መሰለው፡፡
“ምንድነው-- ምንድነው--- ምንድነው…?” አለ ሳይታወቀው፡፡
“አምላኬ ሆይ-- ይህን ያህል ዘመን በመቃብር ቆፋሪነት ሕይወቴን እንድገፋ ያደረከኝ ይኼንን ቀን አስበህልኝ ነው ለካ” ያለልቡ በጉልበቱ ተንበረከከ፡፡
“አምላኬ ሆይ ተመስገን! ተመስገን! የባለቤቴን ጭቅጭቅ ሰምተህ መሆን አለበት ይኼንን በረከት የላከልኝ” የሚስቱ ጐጄ ጦር ምላስ፣ ወደ ወጥ መቅመሻ እና መላሻነት ሲለወጥ፣ የሚኖረውን ሕይወት ለአፍታ በሰመመን ቃኘው፡፡ ምርጊቱ የፈራረሰው የቀበሌ ቤቱ ተቀይሮ ቪላ ቤት ውስጥ ሲኖር፣ በመቃብር ቁፋሮ የቆረፈዱ እጆቹን በወይራ ዘይት እየታሸ ሲዝናና፣ በብርድ የተቆራመደ ገላው በሙቅ ውኃ እየረሰረሰ ሲቀማጠል …እነዚህን ሁሉ ነገሮች ሲያስብ ለመጀመሪያ ጊዜ ያሳለፈው ሕይወት ምን ያህል አስከፊ እንደነበረ ወለል ብሎ ታየው፡፡
“ጐጄ ልክ ነበረችና! ምን ዓይነት አስከፊ ሕይወት ውስጥ ነው የምንኖረው!” ኑሮው አንገሸገሸው፡፡
የሕይወቱን ከግማሽ በላይ ዓመታት በመቃብር ቁፋሮ ማሳለፉን ሊያምን አልቻለም፤ ሙያው፣ አብረውት የሚሰሩት ሰዎች፣ ጐረቤቶቹ፣ የሚኖርበት ሰፈር…አስከፊነት ወለል ብሎ ታየው…ወደፊት የሚኖረውን ህይወት ሲያስብ ልቡ በደስታ ይዘል ጀመር፡፡ በተመስጦ ከተቀመጠበት ስሙ ከውጪ ሲጠራ የሰማ መሰለው፡፡
“ጉልማ --- ጉልማ!!!...” ድንጋጤ መላ አካሉን ወረረው፡፡ ማን ነው ሊጠራው የሚችለው? ሻንጣውን ይዞ ሲገባ ያየው ሰው ይኖር ይሆን? ጥርጣሬ እንደ ግሪሳ ወፍ ወረረው፡፡
“ጉልማ ጉልማ!!!...” ስሙ ተደጋግሞ ተጠራ፡፡
ሻንጣውን ወደ ጥግ አስቀምጦ ድንጋይ ጫነበት፡፡ ግራ ቀኙን በጥርጣሬ እየቃኘ የመቃብር ቤቱን በር ከፍቶ ወጣ፡፡ የቤተክርስትያኑ ዘበኛ ነበር የሚጣራው፡፡ ጉልማን እንዳየው ወደሱ መምጣት ጀመረ፡፡ ከኋላው ሁለት ሰዎች አሉ፡፡ አንድ ወንድ እና አንድ ሴት፡፡
“አላልኳችሁም--- የፈለገ ተአምር ቢፈጠር ይህ ጅላጅል መቃብር ቆፋሪ፣ ከዚህ አይጠፋም” እያለ ዘበኛው ወደ ጉልማ ቀረበ፡፡
“ይኼ ጅላጅል ነው ያልከው አንተ” አለ ጉልማ፣ በደምፍላት ስሜት ተሞልቶ፡፡
ዘበኛው በግርምት እና በድንጋጤ ጉልማን አፍጥጦ አየው፡፡ ጉልማ ሲቆጣ አይደለም ተሳስቶ እንኳን ኃይለ ቃል ሲናገር ሰማሁ የሚል ሰው ታይቶ አይታወቅም፡፡ የጅል ምሳሌ ተደርጐ ቢቀርብ፣ የሞኝ መለያ ተደርጐ ቢጠራ ምንም ቅር የማይለው ፍጡር ነበር ጉልማ፡፡ ዘበኛው በጉልማ ላይ ባየው ድንገተኛ ለውጥ ግራ ተጋብቶ ለአፍታ ዝም ካለ በኋላ፣ ተከትለውት ወደመጡት ሰዎች እያመለከተ መናገር ጀመረ፡፡
“ሥራ ይዤልህ ነው የመጣሁት” አለ ረጋ ብሎ፡፡ “እ…ሟች ከአውሮፓ ነው ሬሳው የሚመጣው--- ጥሩ ቦታ ፈልገህ የመቃብሩን ጉድጓድ እንድታዘጋጅለት ነው የሚፈልጉት--- ያው ዋጋ ተደራደሩ” አለ ለድርድር በሚጋብዝ ሁኔታ እጆቹን ወደ ጉልማና ወደ ሰዎቹ እየዘረጋ፡፡ ጉልማ ግን መልስ ያለው አይመስልም፡፡ ዘበኛውን በንቀት ተመለከተው፡፡ ዘበኛው በጉልማ ሁኔታ ግራ መጋባቱ በግልጽ ያስታውቃል፡፡
“ይኼ ጅል ዛሬ ምን ነካው” አለ ለራሱ፡፡
“እ---የተለመደ ዋጋው 300 መቶ ብር ነው---ባላችሁት ሰዓት ያደርሳል” አለ ዘበኛው፣ ወደ ሰዎቹ እያየ፡፡
“ዋጋው ላይ ችግር የለም፡፡ ጥሩ ቦታ መርጦ በደንብ ያዘጋጅልን፡፡ 1000 ብር እንከፍላለን…ከመንገድ ብዙ ባይገባ ደስ ይለናል” አለች ሴትየዋ፡፡
“ሌላ መቃብር ቆፋሪ ፈልጉ--- እኔ ለመቆፈር ፈቃደኛ አይደለሁም” አለ ጉልማ ጀነን ብሎ፡፡ ዘበኛው በንዴት ጦፈ፡፡ “ጉልማ ዛሬ ጤነኛ አልመሰልከኝም--- ከሶስት እጥፍ በላይ ዋጋ ሰጥተውህ ከዚህ በላይ አምጡ ነው--- ኧረ ተው እናንተ መቃብር ቆፋሪዎች ግን እግዜርን ፍሩ፤ ኧረ ተው” አለ ዘበኛው እያማተበ፡፡
“ለገንዘቡ ችግር የለም--- 2000 ብርም ቢሆን ልንሰጠው እንችላለን፡፡ ብቻ ጥሩ ቦታ እና ከመንገድ ብዙ ያልገባ--- ደህና ሰው መቃብር አጠገብ ይሁን” አለች ሴትየዋ፡፡ ለገንዘብ ብዙ ጭንቅ የለባትም፡፡ በቅርቡ የሞተው ሽማግሌ ባሏ ትቶላት የሄደው በቂ ሀብት አላት፡፡ ከሁኔታዋ ባለቤቷ ዳግም እንዳይነሳ አርቃ ልታስቀብረው የፈለገች ይመስላል፡፡ ለዚህ ደግሞ ብቃት ያለው ቆፋሪ ያስፈልጋል፡፡
“ኧረ ተባረኪ ተባረኪ እንዴት ያለ መቃብር ቆፋሪ መሰለሽ? በሙያው ስለሚተማመን ነው እኮ ትንሽ እንትን ያለው…” አለ ዘበኛው ሥራውን በማምጣቱ የሚያገኘውን ኮሚሽን እያሰበ ተደስቶ፡፡
“እኔ ፈቃደኛ አይደለሁም” አለ ጉልማ በስጨት ብሎ
“ብር ከሆነ ችግር የለውም 3ሺህ ብርም ቢሆን…” ሴትየዋ እልህ የተጋባች ትመስላለች፡፡
“ጉልማ ኧረ ተው እግዜር አይወደውም--- 3ሺህ ብር ለአንድ ክንድ መሬት” ዘበኛው ንዴት ገብቶታል፡፡
“የብሩ ጉዳይ አይደለም--- እኔ መቃብር ቆፋሪነቱን ትቼዋለሁ ---ይኼንን ቀፋፊ ሥራ እስከዘላለሙ ትቻለሁ” አለ ጉልማ ረጋ ብሎ፡፡
“እኮ አንተ መቃብር ቆፋሪነቱን ተውከው?” ዘበኛው ባለማመን ጉልማን እየተመለከተው፡፡
“መቃብር ቆፋሪነትህን ትተህ ምን ልትሆን ነው ነው? አንተ ራስህ ልትሞት አሰብክ?” ዘበኛው ግራ ገብቶት እንደብራቅ ጮኸበት፡፡
“አንተ ሰውዬ አፍህን ብትዘጋ ይሻላል--- አትጩህ” አለ ጉልማ፤ አካፋ የሚያህል እጁን በማስጠንቀቅ ወደ ሰማይ እያነሳ፡፡
ዘበኛው ክፉኛ ደነገጠ፡፡ ጉልማ አንዴ በጥፊ ቢለው መጋኛ አጠናግሮት ከሚደርስበት ጉዳት አስር ጊዜ የበለጠ ጉዳት እንደሚደርስበት እርግጠኛ ነበር፡፡
“አይ…እኔኮ 3ሺ ብር ብዙ ነው ብዬ ነው ጉሌ…አስበው እስቲ 3ሺህ ብር!” ዘበኛው በጉጉት ምራቁን ዋጠ፡፡
“አትሰማኝም?! እኔ መቃብር ቆፋሪ አይደለሁም!!” አለ ጉልማ ወደ ሁሉም በየተራ እያፈጠጠ፡፡
ዘበኛው ጉልማ ያበደ መሰለው፡፡ ሌላ መቃብር ቆፋሪ ማናገር አለበት፡፡ ሰዎቹን እያቻኮለ ወደ መቃብሩ መውጫ ወሰዳቸው፡፡ ጉልማ ግራ ቀኙን እያየ በጥንቃቄ ወደ መቃብር ቤቱ ተመለሰ፡፡ አንድ ሰው በመቃብሮቹ ተከልሎ የሚያየው መሰለው፡፡ ምናልባትም እሱ እስኪርቅ ጠብቆ ገንዘቡን ማንሳት የሚፈልግ ሰው እንዳለ እየጠረጠረ፣ ቀስ ብሎ ወደ መቃብር ቤቱ ተመለሰ፡፡ ሻንጣው መኖሩን አረጋግጦ በእፎይታ ተነፈሰ፡፡
“ሴትየዋ ግን 3ሺ ብር ለመክፈል እንዴት ፈቃደኛ ሆነች?” በአእምሮው ውስጥ ጥርጣሬ ሽው አለበት፡፡ እሱን መቃብር እያስቆፈረች ብሩን ይዛ ልትሞጨለፍ? መጠርጠር ደግ ነው …
“እግዜር ነው ይኼን ብር የላከልኝ! እስካሁን ፍጡሮቹ በቅንነት ሳገለግል መኖሬን ተመልክቶ ሊከሰኝ ነው!” ወደ ሰማይ ቀና ብሎ አመሰገነ፡፡ የመቃብሩ ቤት በደንብ መዘጋቱን ካረጋገጠ በኋላ፣ ሻንጣው ውስጥ ያለውን ብር መቁጠር ጀመረ፡፡ ለሁለት ሰዓት ሳይወጣ መቁጠሩን ቀጠለ …
“ሁለት መቶ ሰማንያ ዘጠኝ ሺህ ሦስት መቶ …” ቆጠራውን እንደቀጠለ ነው፣ ከውጪ ስሙ ሲጠራ የሰማ መሰለው፡፡
“ጉልማ! ጉልማ! …” የሴት ድምፅ ነው፡፡ ብሽቅ አለ፡፡ ሚስቱ ጎጄ ናት፡፡ እንደሁልጊዜው ረፈድ ሲል ለቁርስ የሚቀማምሰውን ይዛለት መጥታ ነው፡፡ ምን ብትነዘንዘው በጉልማ የሚጨክን አንጀት የላትም፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በጎጄ መምጣት ብስጭት አለ፡፡ እንደሌለ መስሎ ዝም ሊላት ፈለገ፡፡ ዝም ካላት ደግሞ የት ገባ ብላ ችግር መፍጠሯ አይቀርም፡፡ የቆጠረውን ገንዘብ ካልቆጠረው ለመለየት በመሀል ድንጋይ ካስቀመጠ በኋላ የመቃብር ቤቱን በር ከፍቶ ወጣ፡፡
“የት ገባህ ደግሞ ዛሬ? መቼም መርመጥመጥ ነው በየመቃብሩ ሥር!” አለች ጎጄ ወደሱ እየቀረበች፡፡
“ጤና የለሽም እንዴ አንቺ ሴትዮ!” አላት ንግግሯ ብስጭት አድርጎት፡፡
ጎጄ በግርምት ሀውልት ሆና መቆም እስኪቀራት ድረስ ተደንቃ አየችው፡፡ ሌላ ሰው መሰላት፣ ጉልማ ሲቆጣ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ጉልማ ስትጠብቅ ስንት ዓመት ኖራለች? የአንድ ጎልማሳ ዕድሜ አልፏል፤ እያለ የሌለው፣ ለምንም ነገር ግድ የማይሰጠው፣ በስድብ እና በሙገሳ መካከል ያለው ልዩነት የማይገባው፣ በዝምታ ካባ ውስጥ ያደፈጠው ጉልማ፣ ነገ የሚባል ነገር በዓይኖቹ ውስጥ የሌሉት ጉልማ! ያ እንደኩሬ የረጋው ጉልማ --- ምን አገኘ?”
“በል ተወው--- ቁርስ ቢጤ አምጥቻለሁ--- አረፍ በልና ቀማምስ!” አለች ጎጄ ለስለስ ብላ፡፡
እንደወትሮው ከአንዱ የመቃብር ሀውልት ላይ ቁጭ ብለው ያመጣችውን ሰሀን አቀበለችው፡፡ ሰሀኑን ከፈተው፣ ሚጥሚጣ እና ቁራሽ ዳቦ ተቀምጧል፡፡ ወሽመጡ ቁርጥ አለ፡፡
“የምትወዳትን ቁርስ ነው ያመጣሁልህ!” አለች ጎጄ ሳቅ እያለች፡፡
“ይኼን መናኛ ቁርስ ነው የምወደው? … በይ ይኼ ቅራቅንቦሽን ይዘሽ ወደምትሄጅበት ሂጅልኝ!” አለ ጉልማ ቁጣ ቁጣ እያለው፡፡
“ይቺን ትወዳለች ጎጄ?! … ጥሩ ቁርስ ከዚህ በላይ ከየት ይምጣልህ? አበዛኸው! ይኼ አፈር ፈንቅለህ የምታመጣው ገንዘብ ቁም ነገር ኖሮት ነው! በዛ ላይ መቅኖ የሌለው!” ጎጄ መንጣጣት ስትጀምር ጉልማ አቋረጣት፡፡
“ይኼ ልቅ አፍሽን ካልሰበሰብሽ ዛሬውኑ ከቤቴ ውጪልኝ! እኔኮ የሚገርመኝ እስካሁን ድረስ እንዴት ችዬሽ እንደኖርኩ ነው!” አለ ጉልማ ኮስተር ብሎ፡፡
“ከቤት ሲወጣ ያልነበረውን ጸባይ ከየት አመጣው?” ብላ ግራ ተጋባች፡፡
ፍርሀት ሰውነቷን ወረረው፡፡ ቃል ሳትተነፍስ ዕቃዋን ሰብስባ ተነስታ ሔደች፡፡ ጎጄን ከኋላዋ አስተዋላት፡፡ ከዚች ሴት ጋር 29 ዓመት ሙሉ መኖሩን ሊያምን አልቻለም፡፡ ፊቷ የተጠባበሰ፣ የተቆረጠ ነጠላ ጫማ የምታደርግ፣ የተቀደደ ቆሻሻ ቀሚስ የለበሰች፣ በዛ ላይ ምላሳም … ከዚህች ሴት ጋር ከአሁን በኋላ መኖር የለበትም፤ ሌላ ሚስት ያስፈልገዋል፡፡ ምናልባትም ልጅ፣ ሰውነቷ እንደ እስፖንጅ የሚለሰልስ፣ ምላሳም ያልሆነች …
ድንገት ዞር ሲል አንበሉ አጠገቧ ቆሟል፡፡
“አጅሬ ---ማታ ጠጅ አበዛህ እንዴ? እኛ ስድስት መቃብር ስንቆፍር አንተ ምንም አልሠራህም አሉ! ለማንኛውም የጠዋት ደንባችንን አድርሰን እንምጣ! … ሁለት ብርሌ ልጋብዝህ!”
አምበሉ አብሮት መቃብር በመቆፈር የሚተዳደር ባልደረባው ነው፡፡ መልኩ ጥቁር ነው፡፡ በዛ ላይ ግዙፍ፡፡ እንደዚህ ሰይጣን ከመሰለ ሰው ጋር ጓደኛ ሆኖ መኖሩ በውስጡ ግርምት ፈጠረበት፡፡
“ሒድ! እኔ ትንሽ ልቆይ!” አለ ጉልማ
“አቤት--- በጠጅ ጨክነህ? ግዴለህም ና እጋብዝሀለው!” አለ አንበሉ ፍርጥም ብሎ
“አልሔድም አልኩህ!” አለ ጉልማ ቆጣ ብሎ፡፡
አንበሉ በግርምት ለአፍታ አየውና ትከሻውን በምን ቸገረኝ ወደ ላይ ሰብቆ “በጠጅ ጨከንክ? ተመስገን! ተመስገን!” እያለ ወደ ጠጁ ተቻኮለ፡፡
የአንበሉን መሔድ ተከትሎ ስሙ ሲጠራ ሰማ፡፡
“ጉልማ! ጉልማ!...” የቤተክርስቲያኑ ጥበቃ ሌሎች ሰዎችን አስከትሎ ወደሱ ሲመጣ ተመለከተው፡፡
“ይኼ ሰውዬ መቃብር ቆፋሪነቴን አቁሜያለሁ ማለት አይገባውም?” ንድድ አለው፡፡
“መቃብር ቆፋሪነቴን አቁሜያለሁ! አይገባህም?” አለ ጉልማ በንዴት ፀጉሩን እየነጨ፡፡
ሰዎቹ ወደሱ ሲቀርቡ በቸልታ ቆሞ ጠበቃቸው፡፡
“ጉልማ እሱ ነው!” አለ ዘበኛው ወደ ጉልማ እየጠቆመ፡፡
“አቶ ጉልማ አንተ ነህ?” አለ ከዘበኛው ጀርባ ከቆሙት ሰዎች መካከል አንደኛው፡፡
ጉልማ ከዘበኛው ጀርባ የቆሙትን ሰዎች አስተዋላቸው፡፡ ሻንጣውን ካገኘ በኋላ፣ ቱታ ለብሰው ስፖርት ሲሠሩ የነበሩት ወጣቶች ናቸው፡፡ ከኋላቸው ፖሊሶች አሉ፡፡
“አቶ ጉልማ ጠዋት ወድቆ ያገኙት ገንዘብ …” ፖሊስ ንግግሩን ሳይጨርስ ጉልማ ራሱን ስቶ ወደቀ፡፡
ከአዘጋጁ - (ከላይ የሰፈረው ታሪክ “በአራጣ የተያዘ ጭን” ከሚለው በቅርቡ ለንባብ የበቃ የአጭር ልብወለድ መድበል የተወሰደ ሲሆን በዝግጅት ክፍሉ መጠነኛ ማስተካከያ ተደርጎበት የቀረበ ነው)

Published in ልብ-ወለድ

በታተመበት ዘመን ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝቶ የነበረው “ጣምራ ጦር” ታሪካዊ ልቦለድ መጽሃፍ፤ ከ30 ዓመት በኋላ ዳግም ታትሞ ሰሞኑን ለንባብ በቃ፡፡ የደራሲ ገበየሁ አየለ የበኩር ሥራ የሆነው ልቦለዱ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ በ1975 ዓ.ም በኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ሲታተም 30ሺህ ቅጂዎች እንደተሸጠለትና ለሦስት ጊዜ እንደታተመ የገለፀው ደራሲ ገበየሁ አየለ፤ አሁን የታተመው በአንባቢያን ጥያቄ መሆኑን ተናግሯል፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ ታትሞ ሲወጣ በአንጋፋው ተዋናይ ወጋየሁ ንጋቱ በሬዲዮ የተተረከው ልቦለዱ፤  የሶማሊያው ጄነራል ሲያድባሬ በኢትዮጵያ ላይ በፈፀመው ወረራ ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው፡፡ ባለፈው ሰኞ ከማተሚያ ቤት የወጣው ባለ 222 ገፁ “ጣምራ ጦር”፤ በ41 ብር ለገበያ የቀረበ ሲሆን በተሰራጨ በሦስት ቀናት ውስጥ ግማሽ ያህሉ እንደተሸጠ  ደራሲው ገልጿል፡፡

ዓላማውን ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን በመከላከል ላይ ያደረገው “ሚስ ዩኒቨርስ” የቁንጅና ውድድር፤ በመጪው መስከረም ወር ለሁለተኛ ጊዜ እንደሚካሄድ አዘጋጁ “ክሬቲቭ ኮሙኒኬሽን ኤንድ ኤቨንትስ” አስታወቀ፡፡ የውድድሩ ምዝገባና ፈተና ነሐሴ 11 እና 12 በፓኖራማ ሆቴል የሚካሄድ ሲሆን መስከረም 10 በራዲሰን ሆቴል በሚካሄደው የ“ሚስ ዩኒቨርስ” የቁንጅና ውድድር፤ አሸናፊዋ ከምታገኘው ሽልማት በተጨማሪ ሕገወጥ ስደትን ለመቀነስ ማስተማርና መቀስቀስ ይጠበቅባታል፡፡

የደራሲ አዳም ረታ ረዥም ልቦለድ “ሕማማትና በገና” ነገ ውይይት እንደሚካሄድበት ሚዩዚክ ሜይዴይ አስታወቀ፡፡ ውይይቱ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመጻሕፍትና ቤተመዛግብት አዳራሽ ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ ለሦስት ሰዓታት ይዘልቃል፡፡ የመነሻ ሃሳብ በማቅረብ ውይይቱን ከሚዩዚክ ሜይዴይ ባለሙያዎች ጋር የሚመሩት የሥነጽሑፍ ባለሙያው አቶ ቴዎድሮስ አጥላው ናቸው፡፡

በኮሜዲያን ታሪኩ ሰማንያ እና ቢኒያም ዳና የተፃፈው “ሀ በሉ” ፊልም ነገ በሀዋሳ ከተማ ባህል አዳራሽ ይመረቃል፡፡ የ100 ደቂቃ ርዝመት ያለው አስቂኝ ፊልሙ፤ በአይዶል ውድድር ለመሳተፍ ከክፍለ ሀገር ወደ አዲስ አበባ በመጡ ሁለት ወጣቶች ላይ ያጠነጥናል፡፡
በፊልሙ ላይ ደራሲዎቹን ጨምሮ ካሙዙ ካሳ ማሚላ፣ ኪችሌ እና ሌሎችም ተውነዋል፡፡ በደቡብ ክልል የአማርኛ ለዛ የተሰራው ይሄ ፊልም፤ አዋሳን ጨምሮ በመላ ሀገሪቱ እንደሚታይ ማወቅ ተችሏል፡፡ ፊልሙ ሙሉ በሙሉ በሐዋሳ የተሰራ ሲሆን ፕሮዱዩሰሩ ቀደም ሲል “ቴክ ኢት ኢዚ” የተሰኘውን ፊልም ፕሮዱዩስ ያደረገው ሻና ፊልም ፕሮዳክሽን እንደሆነ ታውቋል፡፡

Page 11 of 17