­አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ባለፈው እሁድ በሞስኮ 14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና፣ በ10ሺ ሜትር ውድድር የወርቅ ሜዳልያ ካጠለቀች በኋላ፣ በሉዝንስኪ ስታዲየም የልምምድ ስፍራ አካባቢ ባለው መናፈሻ ያደረግነው አጭር ቃለምልልስ እነሆ፡-

በዓለም ሻምፒዮናው ስንተኛው የወርቅ ሜዳልያሽ ነው? (በእጇ የያዘችውን የወርቅ ሜዳልያ እየተመለከትኩ)
አምስተኛው ነው፡፡
በሁሉም ርቀት ማለትሽ ነው? ማለቴ… በ10ሺም በ5ሺም፡፡ በ10ሺ 3ኛሽ ነው አይደለም?
አዎ
ከሳምንት በፊት ሞስኮ ስንገባ፣ በዴሜዶቮ አየር ማረፊያ “ሞስኮ ላይ ስንተኛው ወርቅሽ ነው?” ስልሽ እንዲሁ አምስተኛው ብለሽኝ ነበር፡፡
(ሳቅ) አምስተኛ አልኩ እንዴ፤ ለአምስተኛ ጊዜ ነው የምሮጠው ማለቴ ነው
ያው ነው ብዙም ልዩነት የለውም፡፡ ግን ከውድድሩ በፊት የተበላ ወርቅ አደረግሽው፡፡ ለመሆኑ ከትልልቅ ውድድር በፊት እንደምታሸንፊ ሁሌም እርግጠኛ ነሽ እንዴ?
ህመም ካላጋጠመኝ በስተቀር አዎ፡፡
በዓለም ሻምፒዮና እስከ ዛሬ ካገኘሻቸው የወርቅ ሜዳልያዎች ያስደሰተሽ የትኛው ነው?
በ2007 እ.ኤ.አ በኦሳካው የዓለም ሻምፒዮና ያገኘሁት ነው፡፡ በወቅቱ ታምሜ ብዙ ርቀት ከለቀቅኩኝ በኋላ ያገኘሁት የወርቅ ሜዳልያ ድል በመሆኑ በጣም ያስደስተኛል፡፡ ያኔ በውድድሩ ወቅት ሆዴን አሞኝ ነበር፡፡ እየሮጥኩኝ ልክ አምስት ዙር ካጠናቀቅሁ በኋላ ነው የጀመረኝ፡፡ ውድድሩ ሰባት ዙር ሲቀረው ህመሙ ለቀቀኝ፡፡ ሌሎች አትሌቶች ጥለውኝ ከሄዱ በኋላ ደርሼባቸው ውድድሩን በማሸነፌ ልዩ ደስታ ነበር የተሰማኝ፡፡
በሞስኮው ሉዝንስኪ ስታድዬም በ10ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳልያውን ለመውሰድ የመጨረሻውን ዙር ስትከንፊ ፊትሽ ገፅታ ላይ ልዩ ደስታ ይነበብ ነበር፡፡ ምንድነው ነገሩ?
ወርቁን እንደማገኝ እርግጠኝነት ተሰምቶኝ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ አንቺ በምታስመዘግቢው ውጤት ሁሌም ከመጠን በላይ ይፈነድቃል፡፡ አንቺስ ምንድነው የሚሰማሽ?
ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ሁሌም በድጋፍ ከእኛው ጋር ናቸው፡፡ እናም የምሮጠው የህዝቡን ደስታ እያሰብኩ ነው፡፡ እንደዚያ በመሆኑም ሁሌም ከፍተኛ ሞራልና ክብር ነው የሚሰማኝ፡፡
የ10ሺ ሜትር ንግስት ነሽ ማለት አይቻልም?
እንግዲህ እኔ አላውቅም፡፡ እንደዚህ ነኝ ማለት አልችልም፡፡
በ10ሺ ሜትር በጥሩ ሁኔታ ሮጠሽ የወርቅ ሜዳልያውን ከወሰድሽ በኋላ ብዙ የአትሌቲክስ ባለሙያዎች እና ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በ5ሺም መድገም አለባት እያሉ ነው፡፡ አንቺ ምን ትያለሽ?
እንግዲህ በዓለም ሻምፒዮና እና በኦሎምፒክ በሁለቱም ርቀቶች ደርቤ የመወዳደር ልማዱ ነበረኝ፡፡ ውጤታማም ሆኛለሁ፡፡ ዘንድሮ በ10ሺ ሜትር ብቻ በመወሰኔ የሮጥኩም አልመሰለኝ፡፡ ማጣርያ አድርጌ ገና የፍፃሜ ውድድር ቀርቶኛል ብዬ ነው ሳስብ የነበረው፡፡ ሁለቱንም ርቀቶች መሮጥ ስለለመድኩ ነው፡፡ ፌደሬሽኑ በጠየቀኝ መሰረት፤ ለአዳዲስ አትሌቶች እድል ለመስጠት የሚለውን ሃሳብ ተቀብዬ ነው ላለመወዳደር የወሰንኩት፡፡
በ10ሺ ሜትር እና በ5ሺ ሜትር በዓለም ሻምፒዮና እና በኦሎምፒክ መድረክ ያገኘሻቸው ሜዳልያዎች ስብስብ እኮ ከምርጦቹ ወንድ አትሌቶች ጋር እየተስተካከለ ነው፡፡ በሁለቱ ርቀቶች በኦሎምፒክ ኃይሌን በልጠሽዋል፡፡ ከቀነኒሳም ተስተካክለሻል፡፡ በ10ሺ ግን በአንድ የዓለም ሻምፒዮና ላይ የወርቅ ሜዳልያ ማግኘት ይኖርብሻል፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላ 15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በቤጂንግ ይደረጋል፡፡ ያኔ ምን እንጠብቅ?
በዓለም ሻምፒዮና የሜዳልያ ስብስብ በ5ሺ ሜትር ሁለቱንም እበልጣለሁ፡፡ በ10ሺ አንድ ሜዳልያ ይቀርሻል ያልከው ልክ ነህ፡፡ እንግዲህ የዛሬ ሁለት ዓመት እግዚአብሔር ነው የሚያውቀው፡፡
በአትሌቲክስ ስፖርት በረጅም ርቀት ውድድሮች ከፍተኛ ስኬት ካላቸው የዓለም ሴት አትሌቶች ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ሆነሻል፡፡ ለመሆኑ በስፖርቱ ያገኘሽው ስኬትና ክብር ምን ዓይነት ስሜት ይፈጥርብሻል?
በአትሌቲክሱ የተቀዳጀኋቸው ውጤቶች እና ክብሮች በአገሬ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያስገኙልኝ ክብር እና ዝና ከፍተኛ ደስታ አጐናፅፎኛል፡፡ ድሮ በአገር ቤት ነበርኩ፡፡ ከትንሽ የገጠር ከተማ ነው የወጣሁት፡፡ እዚህ ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሼ ይህን ክብር በማየቴ እና በማግኘቴ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡
ወደ ማራቶን እገባለሁ የምትይው ነገር ከምር ነው?
በሚቀጥለው ዓመት በእርግጠኝነት ማራቶን እሮጣለሁ፡፡ ግን ሙሉ በሙሉ ወደ ማራቶን አልሄድም፡፡ በዓመት ውስጥ አንድ ማራቶን ብቻ ነው ለመሮጥ የወሰንኩት፡፡

ከበቆጂ ከተማ እስከ የዓለም ማማ
ከ10 ዓመት በፊት ጥሩነሽ ዲባባ በ18 ዓመቷ በዓለም ሻምፒዮና ተሳትፋ ፓሪስ ላይ የመጀመርያ የወርቅ ሜዳልያዋን ስትወስድ በአገሯ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ገና ዝነኛ መሆን መጀመሯ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ነው የጥሩነሽ ዝና በዓለማችን ታላላቅ ከተሞች እየገነነ የመጣው፡፡ በሄልሲንኪ፣ ኦሳካ ፣ ቤጂንግ፣ አቴንስ፣ ለንደን፣ ሉዛን፣ ኤደንብራ፣ ፉካካ፣ ደብሊን፣ ብሩክሰልስ፣ ቦስተን፣ ኦስሎና ሌሎች የዓለማችን ግዙፍ ከተሞች የጥሩነሽን አስደናቂ የሩጫ ገድሎች በየተራ አስተናግደዋል፡፡ ሰሞኑን ደግሞ በ14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ10ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳልያ ከተጎናፀፈች በኋላ የጥሩነሽ ዲባባ ስምና ክብር በሞስኮ ደምቋል፡፡ ከሳምንት በፊት በተደረገው የ10ሺሜትር የፍፃሜ ውድድር በሞስኮው ሉዚንስኪ ስታድዬም የተገኙ ስፖርት አፍቃሪዎች፣ ጥሩነሽ ዲባባ ካሸነፈች በኋላ ከመቀመጫቸው ተነስተው በደስታ አጨብጭበውላታል፡፡ የወርቅ ሜዳልያዋን ባለፈው ሰኞ ከተረከበች በኋላም በሞስኮው ሉዝንስኪ ስታድዬም ዙርያ በርካታ የአትሌቲክስ ስፖርት አፍቃሪዎች እና ጀግና ወዳዶች አብረዋት ፎቶ ለመነሳት ሲሻሙ እና ሲጋፉ በአይኑ ለተመለከተ ሰው፣ ጥሩነሽ ዲባባ ምን ያህል ዓለም አቀፍ ጀግና እንደሆነች ለመገንዘብ አያዳግተውም፡፡ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች አትሌቷን አሞጋግሰዋታል፡፡
ዲባባ በትእግስቷ ድል አደረገች ብሏል ሮይተርስ በዘገባው፡፡ ቢቢሲ በበኩሉ፤ ንግስቲቱ ዲባባ ለ5ኛ ጊዜ የዓለም ሻምፒዮን ሆነች ሲል፤ ዴይሊ ኒውስ፤ ዲባባ በ10ሺ ሜትር የዓለም ሻምፒዮና ሃትሪክ መስራቷን፤ ራነርስ ዎርልድ፤ በረጅም ርቀት በበላይነት መቀጠሏን፣ ሌትስራን ደግሞ፤ በ10ሺ ሜትር ተሸንፋ እንደማታውቅ፣ በመግለፅ በአድናቆት ዘግበዋል፡፡
ጥሩነሽ ዲባባ፤ በ14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ10ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳልያ ከተጎናፀፈች በኋላ በረጅም ርቀት “የምንግዜም ምርጥ አትሌት” መሆኗ በከፍተኛ ሁኔታ ጎልቶ ተስተጋብቷል፡፡ በ10ሺ ሜትር በዓለም ሻምፒዮና እና በኦሎምፒክ የተጎናፀፈቻቸው የወርቅ ሜዳልያዎች ብዛት 5 በመድረሱ ብቸኛዋ አትሌት ለመሆን የበቃች ሲሆን ይህን ክብረወሰን ሊጋራት የሚችለው ብቸኛው አትሌት ጃማይካዊው ዩሴያን ቦልት ሆኗል፡፡
በዓለም ሻምፒዮና በ10ሺሜትር ብቻ የወሰደቻቸው የወርቅ ሜዳልያዎች ብዛት 3 የደረሱ ሲሆን ከታዋቂ አትሌቶቹ ኃይሌ ገብረስላሴ እና ቀነኒሳ በቀለ በአንድ የወርቅ ሜዳልያ ነው የምታንሰው፡፡ ሁለቱ አትሌቶች በዓለም ሻምፒዮና በ10ሺ ሜትር እያንዳንዳቸው አራት አራት የወርቅ ሜዳልያዎች ማግኘታቸው ይታወቃል፡፡ በጉዳት ሳቢያ በ2009 እ.ኤ.አ በርሊን ላይ እና በ2011 ዳጉ ላይ በተደረጉ የዓለም ሻምፒዮናዎች ባለመሳተፏ እንጂ ኃይሌንና ቀነኒሳን ጥላ ታልፍ ነበር፡፡ ጥሩነሽ ዲባባ በ10ሺ ሜትር እና በ5ሺ ሜትር ትላልቅ ውድድሮች ከኃይሌ እና ከቀነኒሳ ጋር እኩል ለመሆንና ለመብለጥ የቀራት የአንድ የዓለም ሻምፒዮና ተሳትፎ ብቻ ነው፡፡ ጥሩነሽ ዲባባ በ10ሺሜትር የትራክ ውድድርና በጎዳና ላይ ሩጫ ከዓለም አንደኛ ደረጃ ይዛ የምትገኝ አትሌት ስትሆን በ5ሺ ሜትር ውድድር 2ኛ ደረጃ ላይ ናት፡፡ በሩጫ ዘመኗ በ10ሺ ሜትር ተሸንፋ አታውቅም፡፡ አስራ አንድ ውድድሮች አድርጋ አስራ አንዱንም አሸንፋለች፡፡ 3ቱ የዓለም ሻምፒዮን ሲሆን 2ቱ የኦሎምፒክ ሻምፒዮን ናቸው፡፡
ኃይሌ፣ ቀነኒሳና ጥሩነሽ በ10ሺ እና በ5ሺ ሜትር ውድድሮች
በዓለም ሻምፒዮና በ10ሺ
ኃይሌ 4 የወርቅ፤ 1 የብርና 1 የነሐስ ሜዳልያዎች
ቀነኒሳ 4 የወርቅ ሜዳልያዎች
ጥሩነሽ 3 የወርቅ ሜዳልያዎች
በ5ሺ
ጥሩነሽ 2 የወርቅ ሜዳልያዎች
ቀነኒሳ 1 የወርቅ እና 1 የነሐስ ሜዳልያዎች
ኃይሌ 1 የብር ሜዳልያ
በኦሎምፒክ በ10ሺ
ኃይሌ 2 የወርቅ ሜዳልያዎች
ቀነኒሳ 2 የወርቅ ሜዳልያዎች
ጥሩነሽ 2 የወርቅ ሜዳልያዎች
በ5ሺ
ጥሩነሽ 1 የወርቅና 2 የነሐስ ሜዳልያዎች
ቀነኒሳ 1 የወርቅ እና 1 ብር ሜዳልያዎች
ኃይሌ 0 ሜዳልያ

የደራሲ ሌሊሳ ግርማን ምርጥ ምናባዊ ታሪኮች የያዘው “መሬት ፣አየር፣ሰማይ” መፅሀፍ ለንባብ በቃ፡፡ ከምናባዊ ታሪኮቹ አንዳንዶቹ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ የጥበብ አምዶች ላይ የተስተናገዱ ናቸው፡፡ ሃያ ዘጠኝ ታሪኮችን የያዘው ባለ 207 ገፅ መፅሀፉን ሊትማን ጀኔራል ትሬዲንግ የሚያከፋፍለው ሲሆን ዋጋውም 46 ብር ነው፡፡ ደራሲ ሌሊሳ ግርማ ቀደም ሲል “የንፋስ ህልም” እና “አፍሮጋዳ” የተሰኙ መፅሃፍት ለንባብ አብቅቷል፡፡

ባህላዊውን የቡሄ አከባበር የሚዘክርና ሀይማኖታዊና ባህላዊ ይዘቱ ሳይቀይር በዓለም ቅርስነት የሚመዘገብበትን ዘዴ የሚያውጠነጥን ዝግጅት የፊታችን ሰኞ ምሽት እንደሚቀርብ ኤልቤት ሆቴል አስታወቀ፡፡ የሆቴሉ ስራ አስኪያጅ የእናትፋንታ ውቤ እንዳስታወቁት፤ ፒያሳ በሚገኘው ሆቴል፣ ዝግጅቱ በችቦ ማብራትና ባህሉን የጠበቀ ህብስት ታጅቦ ሲቀርብ ቡሄን የተመለከቱ ሁለት ጥናታዊ ፅሁፎች የሚቀርቡ ሲሆን የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ስራ አስፈፃሚ አባል ደራሲ አፈወርቅ በቀለ የጥንቱን የቡሄ ባህል በተመለከተ የልጅነት ትዝታውን በሆቴሉ ለሚገኙት ሰዓሊያን ፣ደራሲያንና ሌሎች እንግዶች ያጋራል፡፡

 

የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ እና በባህርዳር የሚገኘው የሙላለም የባህል ማዕከል ሚሊኒየሙ የባህል ቡድን በጋራ ያዘጋጁት ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን የሚያወግዝ ኪነጥበባዊ ፕሮግራም እየቀረበ ነው፡፡
የዛሬ ሳምንት በባህርዳር መቅረብ የጀመረው ዝግጅት፤ ግጥሞች፣ሙዚቃ፣ የ25 ደቂቃ ድራማ እንዲሁም ውይይት ተካሂዶበታል፡፡ ተመሳሳይ ዝግጅቶችን የችግሩ ሰለባ በሆኑ ዞኖች እንቀጥላለን ያሉት የባህል ማዕከሉ የፕሮሞሽን ቡድን አስተባባሪ አቶ ሰለሞን ታደሰ ከሌቻ፤ ተዘዋዋሪ የኪነጥበብ ዝግጅቱ ለውጥ ያመጣል ተብሎ ተስፋ እንደተጣለበት ተናግረዋል፡፡ ዝግጅቱ ከሚቀርብባቸው ከተሞች መካከል ወልዲያ፣ወረኢሉ፣መተማ እና ከሚሴ ይገኙበታል፡፡

በቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት መንግስቱ ኃይለማርያም የቤተመንግስትና የስራ ህይወት ዙሪያ የተፃፈው “የሌ/ኮ መንግስቱ ያልተነገሩ ሚስጥሮች” የተሰኘ መፅሀፍ ዛሬ ከማተሚያ ቤት ወጥቶ ለንባብ እንደሚበቃ አዘጋጁ አስታወቁ፡፡ የቀድሞው ልዩ ኃይል አባል እና የፕሬዝዳንት መንግስቱ አጃቢ በነበሩት እሸቱ ወንድሙ ወልደስላሴ የተፃፈው ባለ 120 ገፅ መፅሃፍ ዋጋ 35 ብር ከ45 ሳንቲም ነው፡፡ ለ14 ዓመታት በልዩ ጥበቃነት የሰሩት የመፅሃፉ አዘጋጅ፤ ካሁን ቀደም “ህይወት በመንግስቱ ቤተመንግስት” በሚል ርዕስ ሁለት ቅፅ መጻሕፍትን ያሳተሙ ሲሆን ባሁኑ መፅሀፍ ከተካተቱ ጉዳዮች መካከል መንግስቱ የ1981ዱ መፈንቅለ መንግስት አድራጊዎችን ምን እንዳሏቸው፣ ፕሬዝዳንቱ በትረመኮንናቸው ላይ ብእር መሰል ሽጉጥ እንዲሰራላቸው መጠየቃቸው ወዘተ…ይገኝበታል፡፡

የአዲስ አድማስ ፎቶ ጋዜጠኛ የሆነው አንተነህ አክሊሉ ያነሳቸው ከ30 በላይ ፎቶግራፎች የተካተቱበት “ላይት ኢን ሻዶው” የፎቶግራፍ አውደርእይ ካዛንቺስ በሚገኘው ኦዳ ታወር የፊታችን ሐሙስ ከምሽቱ 12 ሰዓት እንደሚከፈት አዘጋጁ አስታወቀ በኦዳታወር ሶስተኛ ፎቅ በቅርቡ በተከፈተው ኮክ ቺክን ባር እና ሬስቶራንት የሚከፈተው አውደርእይ “ጥበብ፣ ከተማና ገጠር” በሚል መሪ ቃል የሚካሄድ ሲሆን ባለፉት ሰባት ዓመታት ፎቶግራፈሩ በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ተዘዋውሮ ያነሳቸው ምርጥ ፎቶግራፎች ይካተቱበታል፡፡ የፎቶግራፍ ኤግዚብሽኑ እስከ ነሐሴ 20 ለሕዝብ ክፍት ሆኖ ይቆያል፡፡

 

የግእዝ ቋንቋ እንዲያንሰራራ ያለመ ኪነጥበባዊ ዝግጅት ነገ ማምሻውን በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ እንደሚካሄድ አዘጋጆቹ አስታወቁ፡፡ በኮሌጁ የምግብ አዳራሽ የሚቀርቡትን ድራማ፣የጥንታዊ ፅሁፎች ንባብ ፣ቅኔ፣ የግዕዝ ግሰሳ (ትንተና) ፣ጭውውትና ዜናን በግእዝ  የኮሌጁ የግእዝ ቋንቋ ተማሪዎች እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች በህብረት እንደሚያዘጋጁት የጠቀሰው የአዘጋጆቹ መግለጫ፤ ለግእዝ ቋንቋ እና ለኢትዮጵያ የቀድሞ ስልጣኔ አክብሮት ያላቸው ወገኖች ሁሉ በነፃ ዝግጅቱን መከታተል እንደሚችሉ አብስሯል፡፡ የኮሌጁ የግእዝ ክፍለ ትምሕርት ኃላፊ መምህር ዘርአዳዊት አድሓና ስለጉዳዩ ማብራሪያ ጠይቀናቸው፤ ኮሌጁ ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ ቋንቋውን በዲፕሎማ ደረጃ እያስተማረ መሆኑን ገልፀው “በየዓመቱ ደብረ ታቦር ሲከበር ክርስቶስ ለተማሪዎች ምስጢር መግለጡን አስታውሰን ከአብነት ትምህርት ቤቶችን በወረስነው ትውፊት ከበዓለ ደብረታቦር ጋር እናከብረዋለን” ብለዋል፡፡

የዛሬ ሳምንት ሀዋሳ ነበርኩኝ፡፡ የወትሮዋ ሳቂታዋ ሀዋሳ አልነበረችም፡፡ አኩርፋለች፡፡ ሌላ ችግር ገጥሟት ግን አይደለም፡፡ ክረምቱ ነው ያስኮረፋት፡፡
ዝናቡ፣ ቅዝቃዜውና ደመና የሸፈነው ሰማይ ተጫጭነዋት ነበር፡፡ እንደኔ እንደኔ ሀዋሳ ደርሶ አሞራ ገደልን ሳይጐበኙ መመለስ ካለመሄድ እኩል ነው፡፡ እዚህ ስፍራ ዓሳ እንደጉድ ይበላል፡፡ ያውም ቁጥር - ልክ እንደ ስጋ፡፡ የአሳ ቁርጥ ተመጋቢዎች በእንጨት ግድግዳ በተከበበው ዳስ መሳይ ቤት ውስጥ ግፊያውና መረጋገጡን ተያይዘውታል፡፡ በሀዋሳ ሀይቅ ዳር ባለው በዚህ ስፍራ ሰው ከአንድ ቦታ አሳውን ይገዛና እዛው ዳስ ቤት ውስጥ የአሳውን እሾክ እያስወጣ ቁርጡን በሳህን እየያዘ ማባያውን ለማግኘት ሁለት ጐን ለጐን የተቀመጡ ማባያ አቅራቢዎች ጋር መገናኘት ይጠበቅበታል፡፡ አንዱ “ዳጣ” የተባለው እና ከሚጥሚጣ እንዲሁም ከሌሎች ቅመሞች የተሰራ የሚያቃጥል ማባያ ሲሆን (እኔ በጣም ከማቃጠሉ የተነሳ “እንላቀስ” ብየዋለሁ) ሁለተኛው ትንንሽ ክብ የበቆሎ ቂጣዎች ናቸው፡፡ ሁለት ወጣቶች የአሳ ቁርጥ ከግፊያው ውስጥ ይዘው ወጥተው አንዱ ሌላውን፣ “ሂድና ሲዲ ይዘህ ና፣ ታዲያ ስክራች እንዳይኖረው” ሲል አስጠነቀቀው፡፡ ሲዲ ምንድነው ስል ጠየቅሁት አንዱን ወጣት፡፡ “ሲመጣ ታይዋለሽ” አለና ዳጣ ሊያስጨምር መስከረም ወደ ተባለች ዳጣ ሻጭ አመራ፡፡ እኔም ስክራች እንዳይኖረው የተባለውን ሲዲ በጉጉት መጠበቅ ጀመርኩ፡፡ ለካስ ሲዲ የሚሉት የበቆሎውን ቂጣ ነው፡፡ “ስክራች” የተባለው ደግሞ ያረረ እና የተሰነጣጠቀ እንዳይሆን ለማለት የተጠቀሙበት አገላለፅ ነው፡፡

ከወጣቶቹ የእንብላ ግብዣ ቀረበልኝ፡፡ የአሳ ቁርጥ በልቼ ስለማላውቅ ብፈራም “ሲዲ”ውን በዳጣ ግን አልማርኩትም፡፡ ወጣቶቹ ቁርጡን እየበሉ ሳሉ አንዱ “ሲዲውን በርን (burn) አድርገው” ሲል ሰማሁ፡፡ ደሞ ምን ማለት ይሆን አልኩኝ - ለራሴ፡፡ ለካ ቂጣው ስለላቀ ጨምር እና ግዛ ለማለት ነው፡፡ በሳቅ ታጅቤ አብሬያቸው ቆየሁ፡፡ በአሞራ ገደል ከአሳ ቁርጥ ባልተናነሰ የአቮካዶ ቁርጥም እንደ ጉድ ይበላል፡፡ ታዲያ የአቮካዶም ማባያ ዳጣ ነው፡፡ የሲዲ ሻጮቹ ሴቶች ቁጥር በርካታ ነው፡፡ ተደርድረው “ከእኔ ግዛ፣ ከእኔ ግዛ” ይላሉ፡፡ ከሁሉም ዳጣ በመሸጥ ፋታ አጥታ የምትተጋው ግን መስከረም ናት፡፡
መስከረም ላለፉት አራት አመታት በዚህ ስፍራ ዳጣ በመሸጥ ስራ ላይ መቆየቷን አጫውታኛለች፡፡ በዚህ ስፍራ ጠዋት ጠዋት ዳጣ በጅምላም በችርቻሮም ትሸጣለች፡፡ በአካባቢው ከልጅ እስከ አዋቂ ሁሉም የአሳ ቁርጥ በሊታ ነው፡፡ እርግጥ የተጠበሰ አሳም በስፍራው ይገኛል፡፡ ግን ቁርጥ ተመጋቢው በቁጥር ይልቃል፡፡ የተጠበሰ አሳ ከአሞራ ገደል ይልቅ በፍቅር ሀይቅ በኩል ኦሲስ አሳ መሸጫ ውስጥ ይገኛል፡፡ በዚህ ቦታ የአሳ ሾርባው ተጠጥቶ አይጠገብም፡፡
እነሆ ሌላ ትዕይንት፡፡ የአሳ ቁርጥ ሲሰራ የሚጣለውና ትርፍራፊውን የአሳ ስጋ በፌስታል በመያዝ እና በአካባቢው አባ ኮዳ ተብሎ ለሚጠራው ግዙፍ የወፍ አይነት እየወረወሩ በመስጠት ሌላ ስራ የሚሰሩም ታዳጊዎች አስደምመውኛል፡፡ እንግዳ ሆነው ከሄዱ ይህ ወፍ በረጃጅም ማንቁርቱ ስጋውን ለመያዝና ከተቀናቃኙ ሌላው ጓደኛው ለመቅደም የሚያደርገው ዝላይ አይን ያፈዛል፡፡ ብልጣብልጦቹም ታዳጊዎች “ሂዱና ፎቶ ተነሱ” ብለው ወፉ አካባቢ እንዲቆሙ ይነግሩዎታል፡፡ እርስዎም በዚህ ትዕይንት መሀል አንድ ታሪካዊ ፎቶ ልነሳ ብለው ወፉ ስጋ ለመቅለብ የሚያደርገውን ዝላይ እየተመለከቱ ፎቶ ሲነሱ ይቆዩና እግዜር ይስጥልኝ ብለው ሊሄዱ ሲሉ “እንዴ ጋሼ (እትዬ) አስር ብር ይክፈሉ፤ ይህንንም ስራ የምንሰራው እኮ በማህበር ነው” ብለው እርፍ ይላሉ፡፡ እየሳቁም እየተገረሙም ከፍለው ይሄዳሉ፡፡ ሌሎች በርካታ ትዕይንቶችም በዚህ ስፍራ ይገኛሉ፡፡
እነ ሻኪራ በአሞራ ገደል
አሁን ደግሞ ወደነሻኪራ ልውሰዳችሁ፡፡ በዚህ ስፍራ ካስደነቁኝ ነገሮች ሁሉ የእነ ሻኪራ ጉዳይ ነው፡፡ በ2010 የአለም ዋንጫ በደቡብ አፍሪካ በተካሄደ ጊዜ ሻኪራ በስፍራው ተገኝታ “ዋካ ዋካ ዚስ ኢዝ ታይም ፎር አፍሪካ” የሚል ዘፈን ማቀንቀኗ ይታወሳል፡፡ እነሻኪራ ይህን ዘፈን ከነዳንሱ በዚህ ስፍራ አሳምረው ያቀልጡታል፡፡
የቡድን መጠሪያቸው “እነ ሻኪራ” ይሰኛል፡፡ ሂሩት አሸናፊ፣ ሀይማኖት ቶሳ እና መሰረት ኦሳ፡፡ ሂሩትና ሀይማኖት የ7 ዓመት ህፃናት ሲሆኑ የአንደኛ ክፍል ተማሪዎች መሆናቸውን ነግረውኛል፡፡ መሰረት ደግሞ ዕድሜዋ ስምንት አመት ሲሆን የሁለተኛ ክፍል ተማሪ ናት፡፡ እነዚህ ህፃናት ጐስቋላ ኑሮ እንደሚኖሩ በማየት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ አለባበሳቸው፣ ፀጉራቸው አጠቃላይ ሁኔታቸው ኑሯቸው ምቾት የራቀው መሆኑን ይመሰክራል፡፡ ከሁለቱ አንዷ ጫማ አልተጫማችም፡፡ ሂሩት ከላይ የለበሰችው አዳፋ ሹራብ ከጠዋቱ ብርድ ሊከልላት አልቻለም፡፡ ሀይማኖት ደግሞ ፀጉሯ ክፉኛ ቆሽሿል፡፡ ጉብኝቴን ጨርሼ ወዳረፍኩበት ለመመለስ ባጃጅ ኮንትራት ስይዝ አጠገቤ ያለ አንድ ወጣት “እነ ሻኪራ ፈረንጆቹ መጡላችሁ” ብሎ ሲነግራቸው ብን ብለው ወደ ፈረንጆቹ ሮጡ፡፡ ፈረንጆቹ የህፃናቱ ፍላጐት የገባቸው አይመስሉም፤ አልፈዋቸው ሄዱ፡፡ እኔ ጠርቼ አናገርኳቸው፡፡ ባለ ባጃጁም እስካናግራቸው እንደሚጠብቀኝ ነግሮኝ፣ የሻኪራን ዘፈን እየዘፈኑ ብር እንደሚቀበሉ ጠቆመኝ፡፡ እነዚህ ህፃናት አማርኛ በደንብ አይችሉም፡፡ ነገር ግን እየተኮላተፉም ቢሆን መግባባት ችለናል፡፡ “የሻኪራን ዘፈን ከነዳንሱ እንበልልሽ” አሉኝ፡፡
“ቀጥሉ” አልኳቸው፡፡
“በወላይትኛ ዳንስ ይሻልሻል ወይስ በራሷ በሻኪራ?” አማረጡኝ፡፡
“በወላይትኛም በሻኪራም እፈልጋለሁ” አልኳቸው፡፡
“ዋካ ዋካ” ተጀመረ፡፡ ዘፈኑ ወዲያው “ዱርሳ ዱርሳ” ወደተሰኘ ሌላ የአካባቢው ዘፈን ተቀየረ፡፡ አከታትለው የትዕግስት ወይሶን “ገደ ገዳ” ቀጠሉ፡፡ ልጆቹ ነገረ ስራቸው አይን ያፈዛል፤ አንጀትም ይበላሉ፡፡ የሚገርመው እኔ ደንሱልኝ ብያቸው እየደነሱ አይናቸውና ልባቸው ሌላ ጋ ነው፡፡ ሌላ የሚያስደንሳቸው ሰው ፍለጋ በሀሳብ ይባዝናሉ፡፡ መቼ ስራውን እንደጀመሩ ስጠይቃቸው በአንድ ቃል “ዱሮ ነው የጀመርነው” ሲሉ መለሱ፡፡
“አሁን ስንት ታስከፍሉኛላችሁ?”
“የፈለግሽውን ስጭን፤ እኛ ይህን ያህል እያልን አንጠይቅም፡፡”
“እዚህ ስትሠሩ፣ ትምህርታችሁስ?” አልኳቸው፡፡
“አሁን ትምህርት ቤት ዝግ ነው፤ ሲከፈት ግን ከትምህርት ቤት በኋላ እየመጣን እንሰራለን” አሉኝ፡፡
እነዚህን ህፃናት በቀን ስንት ብር እንደሚያገኙና ብሩን ምን እንደሚያደርጉት ጠይቄያቸው ነበር፡፡ በቀን እያንዳንዳቸው ከ10 እስከ 40 ብር እንደሚያገኙና ለእናታቸው እንደሚሰጡ ነገሩኝ፡፡ በዚህ የልጅነት እድሜ ወላጆቻቸውን ይደግፋሉ ማለት ነው፡፡ ከእኔ ጋር እያወራን ዕድሜዋ ገፋ ያለ አንዲት ፈረንጅ ስትመጣ አዩና እሷ ጋ ሄደው ለመደነስ ልባቸው ቆመ፡፡ 10 ብር ሰጥቼ ልሸኛቸው ስል የወደፊት ምኞታቸውን ጠየቅኋቸው፡፡ እንደ ሻኪራ ታዋቂ ዘፋኝና ዳንሰኛ መሆን እንደሚፈልጉ ነገሩኝ፡፡ በት/ቤታቸው እንዲህ አይነት እንቅስቃሴ ያደርጉ እንደሆነም ጠይቄያቸው ነበር፡፡ “ት/ቤት እኛ መደነስ እንፈልጋለን ስንል አይፈቀድልንም፤ እዚህ እየመጣን ነው የምንደንሰው” አሉኝና አመስግነውኝ ወደ ፈረንጇ በቀጫጭን እግሮቻቸው ተፈተለኩ፡፡ ፈረንጇም እግዜር ይስጣት ቆማ በተመስጦ ዳንሳቸውን እየተመለከተች፣ ፎቶግራፍ ስታነሳቸው ነበር፡፡ እቺ ፈረንጅ ከእኔ የተሻለ ጉርሻ እንደምትሸጉጥላቸው በልቤ ተስፋ አደረግሁኝ፡፡ ከሁሌም ያሳሰበኝ ግን የወደፊት ዕጣ ፈንታቸው ነው፡፡ እንደምኞታቸው ይሳካላቸው ይሆን? ብዙ ፈተና ይጠብቃቸዋል፡፡ አንድዬ ይርዳቸው፡፡

Published in ጥበብ
Saturday, 17 August 2013 12:13

ክፍቱ መስኮት

ሄክቶር ሂዩ ሞንሮ (ሳኪ)በ1870 በበርማ ግዛት ተወልዶ በ1916 የሞተ ደራሲ ነው፡፡ አባቱ፤በበርማ መርማሪ ፖሊስ ነበር፡፡ ሳኪ በሎንዶን ጋዜጠኛ ሆኖ በመስራት የፅሁፍ ተሞክሮውን አሀዱ አለ፡፡ የመጀመሪያ የአጭር ልቦለድ ድርሰቶቹ “በዌስት ሚኒስቴር ጋዜት”ታተሙለት፡፡ በቀጣይ ህይወቱ በርካታ የአጫጭር ልብ ወለድ መድበሎች ለአንባቢዎቹ አበርክቷል፡፡ ይህ “ክፍቱ መስኮት” (the open window) የተባለው ነጠላ ልብ ወለድ “The Unbearable Bassington” ከተባለው መድበል የተወሰደ ነው፡፡
                                                  ***
“አክስቴ አሁኑኑ ትመጣለች ሚኒስተር ኔትል….፡፡ እስከዛው ከእኔ ጋር እየተጫዋወትክ እንድትቆይ ተገድደሀል” አለች አንድ “በራሴ ብቁ ነኝ” የምትል የምትመስል የአስራ አምስት አመት ልጃገረድ፡፡
ፍራምቲን ኔትል ፤ወጣቷን ልጃገረድ ባልደለለ፣ እስክትመጣ የምትጠበቀዋን አክስት ባላዋረደ አንዳች የጭውውት አዝማሚያ ሊጠመድ ራሱን አዘጋጀ፡፡ ግን፤ በግሉ እንደዚህ አይነቱ የእንግድነት ቆይታ በማይተዋወቁ ጎረቤቶች መሀል መደረጉ….ለአእምሮ ቀውስ ህመሙ የሚፈይደው ጠቃሚ ነገር መኖሩን ተጠራጥሯል፡፡ በእነዚህ ባይተዋር ሰዎች መሀል የተገኘው ለህመሙ መፍትሄ እንደሚያገኝ በማመኑ ነበር፡፡
“አዎ….አዎ አውቃለሁ ምን እዛ እንደሚጠብቅህ” ብላው ነበር እህቱ፤ አሁን መጥቶ ወዳረፈበት የገጠር መንደር ለመጓዝ ሲሰናዳ፡፡ “አዎ አውቃለሁ እዛ ራስህን ትቀብርና ከማንም ጋር አትገናኝም፡፡ ከብቸኝነትህ የተነሳ የአእምሮ ህመምህ ይብስብሃል፡፡ ስለዚህ እዛ ካሉ ሰዎች ጋር እንድትቀራረብ የትውውቅ ደብዳቤ ልፃፍልህ፡፡ ትዝ ይለኝ ከሆነ እኔ ወደዛ መንደር ስሄድ ከተገናኘሁዋቸው ሰዎች አንዳንዶቹ መልካም ነበሩ”
ሚሲስ ሳፕልተን፤ህመምተኛው ፍራምተን የትውውቅ ደብዳቤውን ይዞ ከተጠጋቸው የመንደሩ ሰዎች አንዷ ናት፡፡ በእህቱ “መልካም” ተብለው ከተጠሩት ሰዎች ምድብ ትሆን? ሲል ፍራምተን አሰበ፡፡
“እዚህ መንደር ካሉ ነዋሪዎች ብዙዎቹን ታውቃለህ?” ስትል የአስራ አምስት አመቷ ልጃገረድ ፍራምተንን ጠየቀችው፡፡
“አንድም ሰው አላውቅም፡፡ እህቴ ከዚህ ቀደም የመነኮሳቱ መኖሪያ ውስጥ ለእረፍት መጥታ ቆይታ አድርጋ ነበር፡፡ ከአራት አመት በፊት ገደማ፡፡ እና እዚህ ሳለች ታውቃቸው የነበሩትን ሰዎች መጎብኘት እንድንችል የትውውቅ ደብዳቤ ሰጠችኝ”
የመጨረሻውን አረፍተ ነገር የተነፈሰበት ቅላፄ “ባትሰጠኝ ይሻለኝ ነበር” የሚል መታከት በውስጡ አዝሏል፡፡ በግልፅ፡፡
“ስለዚህ ስለ አክስቴ ምንም የምታውቀው ነገር የለም?” ብላ በጥያቄ ተከታተለችው፡፡
“ስሟን እና አድራሻዋን ብቻ” አለ እንግድየው፤ወይዘሮ ሳፕተልን ያገባች ትሆን? ወይንስ ባሏን የቀበረች? እያለ ከራሱ ጋር እየተጠያየቀ ነው፡፡ በክፍሉ ውስጥ የሰፈነ አንዳች መንፈስ ባል-ባል….ወንድ-ወንድ ያውዳል፡፡
“አክስቴ፤ ክፉ እጣ ፈንታ የተከሰተው ከሶስት አመታት በፊት ነበር” አለች ልጅቱ፡፡ “እህትህ እዚህ መጥታ ከሄደች በኋላ መሆኑ ነው”
“ክፉ አጋጣሚ?” ተገርሞ ጠየቃት፡፡ እረፍት በተመላው የገጠራማ መንደር ‹ክፉ አጋጣሚ› የሚከሰትበት ስፍራ አይመስልምና፡፡
“በኦክቶበር ወር መስኮቱ እንደዚህ ተደርጎ የተከፈተው ለምን ይመስልሀል?” አለች ኮረዳይቱ፤ወደ መስኩ የሚያመራውን ትልቁን የፍሬች መስኮት ለእሱ እያመለከተች፡፡
“በዚህ ወቅት በተለምዶ አየሩ ሞቃት ነው፡፡ ነገር ግን መስኮቱን ከተከሰተው መጥፎ አጋጣሚ ጋር የሚያገናኘው ምን ነገር አለ?” አለ ፍራምተን፡፡
“በዚህ መስኮት በኩል…ልክ የዛሬ ሶስት አመት….የአክስቴ ባል እና ሁለቱ ወንድሞቹ ለእለታዊ የተኩስ ልምምዳቸው ወጥተው….ሳይመለሱ ቀሩ፡፡ ገላጣውን ምድረ በዳ አቋርጠው ወደ ሚያዘወትሩት…ወደ ሚመርጡት የጠመንጃ መተኮሻ መስክ በማምራት ላይ ሳሉ…ድንገተኛ ደራሽ ወንዝ መጥቶ ጠራርጎ ወሰዳቸው፡፡ መጥፎ ዝናባማ ክረምት ነበር፡፡ አስክሬናቸው የት እንደወደቀ አልታወቀም፡፡ ከሁሉም የሚያሳዝነው የታሪኩ ክፍል ደግሞ በዚህ አኳኋን የደረሱበት ሳይታወቅ መቅረቱ ነው፡፡”
እዚህ ላይ የልጅቱ ድምፅ የቀድሞውን ጠንካራ አንድምታውን አጥቶ ሰብአዊ መሰለ፡፡
“ምስኪኗ አክስቴ አንድ ቀን ቧላ እና ወንድሞቿ ከጠፉበት ተመልሰው ይመጣሉ፤ ብላ ታምናለች፡፡ ከተሰወሩበት፡፡ እነሱ እና አብሯቸው የደረሰበት ያልታወቀው ባለ ቡናማ ፀጉሩ ውሻ አንድ ላይ ሆነው…በዚህ መስኮት በኩል እንደ አወጣጣቸው ተመልሰው ሲወጡ የምታያቸው ይመስላታል፡፡ ለዚህ ነው ፀሀይ እስክትጠልቅ ድረስ መስኮቱ ክፍት የሚተወው፡፡
“ምስኪን አክስቴ….ባሏ እና ወንድሞቿ ወጥተው ለመቅረት ሲሄዱ አኳኋናቸው እንዴት እንደነበር አይረሳትም፡፡ ደጋግማ ነግራኛለች፡፡
“ባለቤቷ ነጩን የዝናብ ካፖርቱን በክንዱ ላይ አድርጎ…..ሮኒ ታናሽ ወንድሟ “ብሬቲ ለምን ትዝያለሽ” የሚለውን ዜማ እያዜመ፡፡ አክስቴ በዛ ዜማ እንደምትበሳጭ ትናገር ስለነበር እሷን ለመተንኮስ ታናሽ ወንድሟ ዜማውን ያዘወትራል….. በዚህ መስኮት በኩል ከጠፉበት ተመልሰው ሲመጡ የማያቸው እየመሰለኝ እኔ እንኳን በፍርሀት ሽምቅቅ እላለሁኝ….”
ልጃገረዲቱ ድንገት እንደ መንቀጥቀጥ ብላ ወሬዋን አቋረጠች፡፡ አክስትየው መዘግየቷን ይቅር እንዲልላት እንግዳዋን እየጠየቀች ወደ ሳሎን ቤቱ ገባች፡፡ አክስትየው በመምጣቷ ፍራምተንን ግልግል ተሰማው፡፡ በልጅቷ ወሬ ተጨንቆ ቆይቶ ነበር፡፡
“ቬራ እያጫወተችህ እንደቆየች እገምታለሁ” አለችው፤ወይዘሮ ሳፕልተን፡፡
“መሳጭ ነበረች” አለ ፍራምተን፡፡
“መስኮቱ ክፍት በመሆኑ እንደማትረበሽ ተስፋ አደርጋለሁ” አለች ወይዘሮ ሳፕልተን ጠበቅ ባለ ቅላፄ፡፡ “ባለቤቴ እና ወንድሞቼ ከተኩስ በቀጥታ ወደ ቤታችሁ የሚመለሱት በመስኮቱ በኩል ነው፡፡ ወደ ረግረጉ ቦታ ወርደው ስለሆነ የሚመለሱት በጨቀዩ ጫማዎቻቸው ምንጣፌን ማበላሸታቸው አይቀርም፡፡ የእናንተ ወንዶች ነገር እንደዛ ነው አይደል?”
ስለ ተኩስ ልምዳቸው …..እየተመናመኑ ስለመጡት የአደን ወፎች… እንደዚሁም በክረምት ዳክዬዎች እንደሚበዙ… እና ወዘተ በማውራት ተንጣጣች፡፡ ለፍራምተን ይህ ሁሉ ወሬዋ አሰቃቂ ሆነበት፡፡ የወሬዋን አቅጣጫ ወደ ሌላ አርዕስት ለመቀየር በፅኑ ተፍጨረጨረ፡፡ ግን ስኬታማ አልሆነም፡፡ ወይዘሮዋ፤ ለፍራምተን ጭንቀት ቁብ እንዳልሰጠች አስታወቀባት፡፡ አይኖቿ በተደጋጋሚ በእርሱ ላይ አልፈው፣ በተከፈተው መስኮት፣ ከመስኮቱ ባሻገር ወዳለው መስክ ይማትራሉ፡፡ ከሶስት አመት ባሻገር ወደነበረው ጊዜ፡፡
ክፉው አጋጣሚ በሚዘከርበት ሶስተኛ አመት፣ ፍራምተን በዚህ ቤት ውስጥ እንግዳ ሆኖ መገኘቱ መጥፎ አጋጣሚ ሆነበት፡፡
“ዶክተሮቼ ሙሉ እረፍት ማድረግ እንዳለብኝ በአንድ ላይ ተስማምተዋል፡፡ ተስማምተው እረፍት አዝዘውልኛል” አለ ፍራምንተን፡፡ “ሥነ ልቦናዬን ከሚያስጨንቅ ማንኛውም አይነት የሥሜት ጡዘት እንድታቀብ ወይንም ሀይል የሚጠይቅ ምንም አይነት የአካል እንቅስቃሴ እንዳላደርግ አስጠንቅቀውኛል” በማለት የጤና እክሉን ይፋ አደረገ፡፡ ከቁጥጥሩ ውጭ ለመውጣት የሚታገለውን ግራ መጋባት ለማረጋጋት እየጣረ፡፡
ከአጋጣሚ ትውውቅ የተገኙ ሰዎች አንዱ የሌላውን ሰው ህመም እና ድክመት…..ለማወቅ ጉጉት እንዳላቸው ያውቃል፡፡
“ምን አይነት ምግብ እየተመገብኩ ማረፍ እንዳለብኝ ግን ሀኪሞቹ እርስ በእርስ ስላልተስማሙ ትዕዛዝ አልሰጡኝም”ብሎ ፍራምተን ቀጠለ፡፡
“ነው?” አለች ወይዘሮ ሳፕልተን ማዛጋትን እንደ ማፈን በመሰለ ድምፅ፡፡
ቀጥላ ግን ድንገት ፈካ አለች፡፡ በንቁ አስተውሎት፡፡ ፍራምተን እያወራት ላለው ነገር አልነበረም የነቃችው፡፡
“ይኸው መጡ በስተመጨረሻ!” ብላ ጮኸች፡፡ “ልክ ደግሞ ሻይ በመጠጫችን ሰአት፣በጭቃ እስከ አይናቸው ድረስ የተዘፈቁ አይመስሉም!”
ቀላል የማይባል መንቀጥቀጥ ፍራምተንን ሰበቀው፤በመቀጠል ወደ አስራ አምስት አመቷ ልጃገረድ ዞረ “ምንድነው እየተከሰተ ያለው?” የሚለውን ጥያቄ ከነመልሱ እንድትለግሰው የሚለማመጥ አሳዛኝ የእይታ ተማጽኖ ወረወረባት፡፡ ልጃገረዲቱ ከመስኮቱ ውጪ እየተመለከተች ነበር፡፡ በድንጋጤ ክው ብላለች፡፡
ፍራምተን ስም አልባ በሆነ የፍርሀት ጥፊ ተመትቶ ከመቀመጫ ተጠማዝዞ ዞረ፡፡ ወደ መስኮቱ ተመለከተ፡፡ ልጅቱ እየተመለከተችበት ወዳለው አቅጣጫ፡፡
እየጠለቀች ባለችው የጀንበር ውጋገን ሶስት ሰዎች ወደ መስኮቱ አቅጣጫ በማምራት ላይ ናቸው፡፡ ሶስቱም በብብታቸው ጠመንጃ ይዘዋል፡፡ ከመሃከላቸው አንዱ በትከሻው ላይ ነጭ ካፖርት ደርቧል፡፡ የተዳከመ የሚመስል ቡና አይነት የፀጉር ቀለም ያለው ውሻ፣ ከእግራቸው ስር ኩስ-ኩስ ይላል፡፡
ሦስቱ ሰዎች ያለ ምንም ድምፅ ወደ ቤቱ ተጠጉ፡፡ ሸካራ የጎረምሳ ድምፅ “ብሬቲ ለምን ትዘያለሽ?” ብሎ በጩኸት አዜመ፡፡ ፍራምተን በእውር ድንብር ከዘራውን እና ባርኔጣውን ካስቀመጠበት አነሳ…. በኮሪደሩ በኩል ወደሚያስወጣው በር….ከዛ በጠጠራማው የደጅ ጥርጊያ በኩል አድርጎ ፈረጠጠ፡፡ ብስክሌት እያሽከረከረ በመግቢያው የሚያልፍ ሰው ከፍራምተን የሽምጥ አመጣጥ ጋር በግንባር እንዳይላተም ቁጥቋጦ ውስጥ አቅጣጫውን ስቶ ለመግባት ተገደደ፡፡
“ይኸው መጣን የኔ ውድ!” አለ ነጩን ካፖርት የደረበው ሰውዬ፤በፍሬንች መስኮቱ በኩል ገና ከመግባቱ፡፡ “ጭቃም ነበረ፣ነገር ግን አብዛኛው መሬት ደረቅ ነው፡፡ ማነው ይሄ እኛ ስንመጣ ፈርጥጦ የወጣው ሰውዬ?”
“በጣም የተለየ እና ግራ የሚጋባ ሰውዬ ነው፡፡…… ፍራምተን ኔትል ይባላል” አለች ወይዘሮ ሳፕልተን፡፡ “ስለ ህመሙ ብቻ ነው ማውራት የሚችለው፡፡ እና እናንተ ስትመጡ …..አንድም ጥሩ አሊያም የይቅርታ ቃል ሳይተነፍስ …..ፈርጥጦ ጠፋ፡፡ የሆነ የሙት መንፈስ ያየ እኮ ነው የሚመስለው….”
“ምናልባት በውሻው ምክንያት ሊሆን ይችላል” አለች ልጃገረዲቱ ረጋ ብላ፡፡ ቀጠለችና “ውሻ እንደሚፈራ አጫውቶኛል….በአንድ ወቅት በጋንጃ ሀይቅ አቅራቢያ ውሾች አሳድደውት መቃብር ቤት ለመሸሸግ ገብቶ ነበረ፡፡ እና ሌሊቱን ለመቃብር በተቆፈረ ጉድጓድ ገብቶ ለማደር ተገድዶ ነበር፡፡ ውሾቹ በጉድጓዱ አፍ ዙሪያ ከበው ሲጮሁ፣ ሲያጓሩበት እና አረፋቸውን ሲደፍቁበት….ነጋለት፡፡ ማንንም ሊያቀውስ የሚችል ነገር እኮ ነው ያጋጠመው…” አለች ልጃገረዲቱ፡፡ ያለ ምንም ቅድመ ዝግጅት ታሪክ ፈጥራ መናገር ልዩ ተሰጥኦዋ ስለሆነ፡፡

 

Published in ልብ-ወለድ

ኮሜዲያንና ድምፃዊ ታሪኩ ሠማኒያ ሸሌ
ታሪኩ ሰማኒያ ሸሌ፤ ሀዋሳ ውስጥ ተወልዶ ያደገ ድምፃዊ፣ ኮሜዲያንና ተዋናይ ነው፡፡ “ጫት ያመረቅናል” በሚለው ነጠላ ዜማው የሚታወቅ ሲሆን መድረክ ላይ በሚያቀርባቸው ቀልዶቹ በተለይ በሀዋሳ ከፍተኛ እውቅናን አትርፏል፡፡ ወጣቱ በቅርቡ ሻና ፊልም ፕሮዳክሽን ፕሮዱዩስ ያደረገውን “ሀ በሉ” የተሠኘ የኮሜዲ ዘውግ ያለው ፊልም ከጓደኛው ቢኒያም ዳና ጋር የፃፈ ሲሆን የኦሊሴን ባህሪ ወክሎ በመሪ ተዋናይነት ተውኗል፡፡“ሸሌ” በተሰኘው የአያቱ ስም ምክንያት ስለገጠሙት ችግሮች፣ በአርቲስትነት ህይወቱና በወደፊት ህልሞቼ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ በሀዋሳ አግኝታ አነጋግራዋለች፡፡

 እንተዋወቅ?

ስሜ ታሪኩ ሰማንያ ሸሌ ይባላል፡፡ ተወልጄ ያደግሁት እዚሁ ሃዋሳ ውስጥ ነው፡፡
ሸሌ የአያትህ ስም ነው? ትርጉሙ ምን ማለት ይሆን?
ረጅም ሳቅ… አንቺ ለምን የአያቴ ስም ላይ ትኩረት እንዳደረግሽ ገብቶኛል፡፡ ሸሌ የሚለው ቃል በህብረተሰቡ ምን ያህል ከባድና ምን ማለት እንደሆነ ስለምታውቂ ነው፡፡ ለማንኛውም ሸሌ የአገር ስም ነው አርባ ምንጭ አካባቢ የምትገኝ ትንሽ ከተማ ናት፡፡ እናም የአያቴ እናት እርጉዝ ሆነው በዚያ አካባቢ ሲያልፉ ድንገት ምጥ ይዟቸው አያቴ እዛች ከተማ ውስጥ በመወለዳቸው ነው ሸሌ የሚል ስያሜ ያገኙት፡፡
በአሁኑ ሰዓት ኮሜዲያን፣ ዘፋኝና ተዋናይ ከመሆንህ ባሻገር “ሀ በሉ” የተሰኘ ፊልም ከጓደኛህ ቢኒያም ዳና ጋር ጽፈህ ለእይታ አብቅተሃል፡፡ እስቲ ስለ ኪነ ጥበብ ህይወትህ ትንሽ አጫውተኝ?
የኪነ - ጥበብ ህይወቴ የሚጀምረው ከቤተ - ክህነት ነው፡፡ በሀዋሳ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ - ክርስቲያን ውስጥ ዘማሪ ነበርኩኝ፡፡ በቤታችን ውስጥ ለሀይማኖት ከሚሰጠው ከፍተኛ ግምት የተነሳ ቴፕ ለሬዲዮ ካልሆነ ሙዚቃ እንኳን ማዳመጥ አይፈቀድም ነበር፡፡ እኔ ግን የሙዚቃ ፍላጐት ስለነበረኝ ቤተሰቤን ፈርቼ ሌላ ሰፈር እየሄድኩ እዘፍን ነበር፡፡
ያኔ በልጅነትህ ስትዘፍን ቅጽል ስም እንደነበረህ ሰምቻለሁ፡፡ ንገረኝ እስቲ?
ልክ ነሽ ቅጽል ስሜ “ሻላ ባንድ” ይባል ነበር፡፡ ስታዲየም ውስጥ ገብቼ ብቻዬን ስዘፍን ነው ይህን ስም ያወጡልኝ፡፡ በስታዲየሙ የጨዋታው ግማሽ 45 ላይ እረፍት ሲሆን “ሻላ ባንድ እረፍት ላይ ነው” ብለው ቁም ሸንኮራ ይሰጡኛል፡፡ እኔም እስከቻልኩ ሸንኮራዬን ከበላሁ በኋላ ወደ ስራዬ እገባለሁ፡፡
መቼም አንድ ቁም ሸንኮራ ከበላህማ አጥር አፈረስክ እንጂ በላህ አይባልም አይደለ?
(በጣም እየሳቀ) ያው በይው… አጥር አፈረስክ ነው ያልሽኝ… ልክ ነሽ አጥር ማለት ነው፡፡
መቼ ነው ኮሜዲያን መሆን እንደምትችል ያወቅኸው?
በ1991 ዓ.ም መከላከያ ያወጣውን ማስታወቂያ በሬዲዮ ሰምቼ ሄድኩኝ፡፡ ግን እድሜዬ በወቅቱ ትንሽ ስለነበር ማደግና ማሻሻል እንዳለብኝ ተነግሮኝ ተመለስኩና እዚሁ ሃዋሳ ውስጥ በአማተር ክበባት ውስጥ መሳተፍ ጀመርኩኝ፡፡ ያኔ ግን ኮሜዲያን እና ዘፋኝ እንደምሆን እርግጠኛ ነበርኩ፡፡ እንደነገርኩሽ ከሰፈሬ ርቄ ሌላ ሰፈር እየሄድኩኝ እዘፍን ነበር፡፡ በፀረ -ኤድስ ክበባትም ውስጥ እንዲሁ ተሳትፎ ነበረኝ፡፡ በዚህ በዚህ አሁን ላለሁበት እደርሳለሁ የሚል እምነት ነበረኝ፡፡
በትክክል መድረክ ላይ መዝፈን የጀመርከውስ መቼ ነው?
ከቢጂአይ ድራፍት ባንድ ጋር ስራ ጀመርኩኝ፡፡ በዘፈንና መድረክ በመምራት የቢጂአይን ምርቶች አስተዋውቅም ነበር፤ እዚሁ ሃዋሳ ውስጥ፡፡ እግረ መንገዴንም ቀልዶችን አቀርብ ነበር ኮሜዲያንነትን ሳስብ ሞዴሌ ተስፋዬ ካሳ ነው፡፡ በጣም በጣም ነው የማደንቀው እንደሱ ያለ ኮሜዲያን ድጋሚ የማይ አይመስለኝም እና ከቢጂአይ ጋር ነው መድረክ ላይ መቆም የጀመርኩት፡፡
እንደሚታወቀው ተስፋዬ ካሳ ኮሜዲያን ብቻ ሳይሆን ድምፃዊም ነበር፡፡ ከዚህ ተነስተህ ነው ሁለቱንም አጣምረህ የቀጠልከው?
በትክክል! ተስፋዬን ከማድነቄ የተነሳ የእርሱን ስራዎች በጣም እከታተልና አዳምጥ ነበር፡፡ የእሱን ስራዎች ስከታተል ዘፋኝ እንደነበርም አወቅሁኝ፤ ያን ጊዜ ሁለት ቦታ ይከፈል የነበረው ልቤ ተረጋጋ፡፡ ወደ ሙዚቃው ጓዜን ጠቅልዬ ልግባ ወይስ ወደ ኮሜዲያንነቱ እያልኩ ልቤ መንታ መንገድ ላይ ነበር፤ ሁለቱንም ጐን ለጐን ማስኬድ እንደሚቻል ከተስፋዬ ነው የተማርኩት፡፡ አሁን ከሙዚቃና ከኮሜዲያንነት በተጨማሪ ተዋናይና የፊልም ደራሲ እስከመሆን ደርሻለሁ፡፡ ለሙያሽ ፍቅር ካለሽ የሚያቅት ነገር የለም፡
እንደሚመስለኝ መጀመሪያ የታወቅኸው “ጃ ያስተሰርያል” የተሰኘውን የቴዎድሮስ ካሳሁንን ዘፈን “ጫት ያመረቅናል” በሚል ከዘፈንክ በኋላ ነው…
አዎ ትክክል ነው፡፡ የዚህ ዘፈን ለአደባባይ መብቃት በራሱ ትንግርት ነው፡፡
እንዴት?
እየሁልሽ… ጫት ያመረቅናል የተሰራው በሀዋሳ ዩዝ ካምፓስ የወጣቶች ማዕከል ውስጥ ነው፡፡ በዚህ ማዕከል ውስጥ የተለያዩ የኪነ ጥበብ ስራዎች ይሰራሉ፡፡ ሰርከስ እና ከሰርከስ ጋር በተያያዘ ኦፔራ ሾው ይካሄዳል፡፡ እና አንዴ “ጐልደን ኤግ” የሚል ኦፔራ ሾው ተዘጋጅቶ ይህ ሾው በአንድ ሱሰኛ የሆነ ገፀ - ባህሪ ላይ ያጠነጥን ነበረ፡፡ ሾው ላይ ያለ ንግግር (“ማይም”) እያደረጉ ይሰሩ ስለነበር በሱስ ዙሪያ የማጀቢያ ሙዚቃ እንድሰራ ተጠየቅሁኝ፡፡ እኔ እንግዲህ በሙዚቃው በኩል ቴዲ ተጽእኖ ፈጣሪ ነው ብዬ የማስብና የማደንቀው በመሆኔ ዘፈኖቹን በማስመሰል እጫወት ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ሰው ሊቀበለውና ተጽእኖ ሊፈጥር በሚችል መልኩ “ጃ ያስተሰርያል”ን “ጫት ያመረቅናል” በሚል፡፡ በወቅቱ የሰራሁት ለዚያ ሾው ብቻ እንጂ ለገበያ አልነበረም፡፡
ግን እኮ በየሞባይሉ ሁሉ ተለቆ ሲደመጥ ነበር፡፡ እንዴት ለገበያ አልነበረም ትላለህ?
እኔ ያኔ ለተዘጋጀው ሾው ተጠቅመን እንዲጠፋ ነበር የፈለግሁት፡፡ አሁን አሜሪካ የሚገኝ ተስፋዬ የተባለ ጓደኛዬ,፣ (የአይኪዶ ስፖርት ኤክስፐርት ነበር) አሬንጅመንቱን የሰራልኝ፡፡ ይሄ ነገር ከተወደደ ለምን አትለቀውም አለኝ፡፡ እኔ ግን ቴዲ አፍሮን በጣም አከብረው ስለነበር መጠየቅ አለብኝ በሌላ ድምፅና ቅንብር እሰራዋለሁ የሚል አቋም ያዝኩኝ፡፡ በዚህ አቋም ላይ እንዳለሁ አማሮ ኬሌ ለስራ ሄጄ አንድ የአሮኬሌ ሰው አገኘኝ፡፡ እኔ የኮሬ ዘፈን ስዘፍን መጣና እያደነቀኝ እያለ ስልኩ ጠራ፡፡ መጥሪያው ደግሞ “ጫት ያመረቅናል” የሚል ነው፡፡ በጣም ደነገጥኩኝ፡፡
ከዚያስ? ከቴዲ አፍሮ በኩል ችግር አልገጠመህም?
በጣም ደግንጬ ከየት እንዳገኘው ስጠይቀው,፣ “አገር ምድሩ ሰምቶ የጨረሰውን እንዴት የት አገኘኸው ትለኛለህ?” አለኝ፡፡ እኔ ይህ ሙዚቃ ያለበት ኮምፒዩተር በፓስዎርድ እንደተቆለፈ ነበር የማውቀው፡፡ ሰውየውም ሀዋሳ አንድ ሞባይል ቤት ነው ያስጫንኩት አለኝ፡፡ ለካስ እዚህ ሀዋሳ አንድ ጆኒ ሞባይል የሚባል ሞባይል ሴንተር ያለው ጓደኛዬ ነው የለቀቀው፡፡ ያስፈመሰኝ መስሎት አሳነሰኝ (ያሳወቀኝ መስሎት ለማለት ነው) ከዚህ በኋላ አንዴ አምልጧል ከቴዲ በኩል ለሚመጣብኝ ጥያቄ መልስ የሚሆነኝን ነገር ማዘጋጀት ጀመርኩ፡፡ ሌላ አማራጭ የለኝም፡፡ ከዚያም ቴዲ ደወለ፤ ሁለት ቴዲ የሚባሉ ጓደኞች ነበሩኝ፡፡ እነሱ እንዳልሆኑ ብዬ በደንብ ጠየቅኩኝ “ቴዲ አፍሮ ነኝ” አለኝ፡፡ ደነገጥኩኝ፡፡ ስልኬን ከአርቲስቶች እንዳገኘ ነገረኝ፡፡ ተቀያየምን፡፡ ከዚያ አዲስ አበባ ሄጄ በወቅቱ “ዘማይንድ” የተባለ መፅሄት ላይ በሰጠሁት ቃል ይቅርታ ጠየቅኩት፡፡ በዚህ ተቋጨ፡፡
እንደሰማሁት ሙዚቃው ጫትን የሚያወድስ ሳይሆን የሚያወግዝ ነው፡፡ ቅመህ ታውቃለህ?
በፊት አልፎ አልፍ እሞክር ነበር፡፡ በነገርሽ ላይ የጫትን አስከፊነት፣ ከምርቃና በኋላ የሚፈጥረውን ነገር ለመግለፅ የግድ መቃም የለብሽም፡፡ የጫት ሱሰኛ ያልጠበበውን ጫማ ጠበበኝ ብሎ ይሸጣል፣ የሚቅምበት ካጣ የቤተሰቡን ንብረት ይሸጣል፡፡ አልፎ ተርፎም እስከ ስርቆት ይሄዳል፡፡ ይህ አይነት ጉዳት አለው ብሎ መልዕክት የሚያስተላልፍ ነው “ጫት ያመረቅናል” ብዬ የዘፈንኩት፡፡
በቅርቡ አንተና ቤሾ የተባለ ወጣት (“ጉዱ ማሌ” በተሰኘ ዘፈኑ ይታወቃል፡፡) በይሳቃል ኢንተርኔይመንት ተጋብዛችሁ ሸራተን ጋዝ ላይት ውስጥ ስራችሁን አቅርባችኋል፡፡ የታዳሚው አቀባበል ምን ይመስል ነበር?
ሸራተን ውስጥ ሰው እንደዚያ በጣም ሲስቅ ሳይ በጣም ነው የገረመኝ፡፡ በጣም ጥሩ ምላሽ ነው ያገኘነው፡፡ “በርቱ አሪፍ ነው” ያሉን አሉ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለስራው የጋበዙንን እናመሠግናለን፡፡
ሰውን ማሳቅ ከባድ ነው፤ ከፍተኛ የፈጠራ ችሎታና ጥረትን ይጠይቃል፡፡ አንተ በዚህ በኩል ምን ያህል እየተጋህ ነው?
አንድ ትልቅ ነገር አንስተሻል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሰውን ማሳቅ ከባድ ነው፡፡ ሰው ኑሮው ተጭኖታል፤ ከተስፋ ይልቅ በትዝታ መኖር የጀመረበት ወቅት ነው፡፡ “ቁርጥ በኛ ጊዜ ቀረ” “ጤፍ በኛ ጊዜ ቀረ” የሚል ሰው በርክቷል፡፡ እንዲህ ያለ ጫና ያለበትን ሰው ለማሳቅ አንቺ ማማጥ አለብሽ፡፡ እኔ ሰው ሳቅ እንደሚፈልግ ሸራተን ስራዬን ባቀረብኩበት ወቅት ተመልክቻለሁ፡፡ በሳይንሱም ሳቅ ለብዙ ነገሮች ጠቃሚ ነው፤ ይህን ለማሳካት በጣም እየተጋሁ ነው፡፡ በሀዋሳ ብቻ ነበር የምታወቀው አሁን ከጓደኞቼ ጋር ወደ አዲስ አበባም እየመጣሁ መስራት ጀምሬያለሁ፡፡ ሁሌም መትጋትና መፍጠር ወሳኝ እንደሆነ ስለማምን፣ በአሁኑ ሰዓት በየቀኑ ሶስትና አራት ፈጠራዎችን እሠራለሁ “ታሪኩ ምን አዲስ ነገር አለ” ሲሉኝ፤ ደረቴን ነፍቼ መናገር እችላለሁ፡፡
ሸራተን ላይ ስራህን ስታቀርብ ስምህን በእንግሊዝኛ ተርጉመህ ሰውን አስቀኸው እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡ እስኪ ለአንባብያን ተርጉሞላቸው…
የዛን ቀን እንዲህ አይነት ስም በአለም የለም፣ በጊነስ ላይ መመዝገብ አለበት ብለው አስተያየት የሰጡ ነበሩ፡፡ ስሜ ታሪኩ ሰማኒያ ሸሌ ነው፤ በእንግሊዝኛ ደግሞ “ሒስትሪ ኤይቲ ባር ሌዲ” ይባላል ስላቸው፣ ህዝቡ መሳቁን ማቋረጥ አልቻለም ነበር፡፡ እንደገና በአራድኛ ስሙን እንጥራው አሉ፡፡ “ታሪኩ ጋብቻ ባርሌዲ” ይሁን ተባለ፡፡ ያው ጋብቻ ሰማንያ ስለሚባል ለማንኛውም በእለቱ ስሜ አወዛጋቢና የስም “ኦሾ” ሆኖ ነበር ያመሸው፡፡
ከአያትህ ስም ጋር በተያያዘ የገጠሙህ ፈተናዎች እንዳሉ ሰምቻለሁ፡፡ እውነት ነው?
የሚገርምሽ ፋይናንስ ሀላፊ ተሳደብክ ተብዬ ከመንግስት መስሪያ ቤት ተገፍትሬ ወጥቻለሁ፡፡ የአያቴን ስም በመናገሬ ነው ተገፍትሬ የወጣሁት፡፡ የአያቴን ስም ስትጠይቀኝ ኮስተር ብዬ “ሸሌ” አልኳት፡፡ “እንዴት ሸሌ ትለኛለህ” ብላ ጮኸች፤ ተገፍትሬ ወጣሁ፡፡ ከዚያም በስንት መከራ ነው መታወቂያ አሳይቼ ያመኑኝ፡፡
ከአባትህ ሞት ጋር በተያያዘ ስማቸው ሲነሳ ብዙ ነገር መባሉን ከጓደኞችህ ሰምቻለሁ፡፡ እስኪ አጫውተኝ?
በነገርሽ ላይ አባቴ አቶ ሰማኒያ ሸሌ ከ1986 ወዲህ እስከሞተበት ጊዜ ድረስ ጭስ አልባው ኢንዱስትሪ በሚባለው በሽመና ስራ ላይ ብዙ እውቅና ነበረው፡፡ የሽመና ኢንዱስትሪ አስፋፍቶ ከ30 በላይ ሰራተኞች ያስተዳድር ነበር፤ ብዙ ሰው ያውቀዋል፡፡ በአጋጣሚ በወጣበት ይርጋለም ላይ በመኪና አደጋ ይሞትና አስክሬኑ መምጣቱ ሲሰማ፣ ሀዋሳ ላይ የህዝቡ ጩኸት ከዳር እስከዳር ቀውጢ ሆነ፡፡ የአማረ ሆቴል ባለቤት “አንተ አቡሽ ምንድነው ጩኸቱ?” ብለው አንዱን ልጅ ሲጠይቁት “ሰማኒያ ሸሌ በመኪና አደጋ ሞተ” ይላቸዋል፡፡ “ከአንድ መኪና ይሄ ሁሉ ሴት በአንዴ? ከካቻማሊ የበለጠ ከ60 ሰው በላይ የሚጭን መኪና አለ እንዴ? እንዴት በአንድ ጊዜ ሰማኒያ ሴቶች ይሞታሉ” ብለው እንደነበር በለቅሶው ሰሞን ሰምቻለሁ፡፡ አንዱ ደግሞ ሰማኒያ ሸሌ ሞተ ሲባል “የሀዋሳ ወንድ ጦሙን አደረ በለኛ” ብሎ ቀልዷል አሉ፡፡ ብቻ በአያቴ ስም ብዙ አስገራሚና አስቸጋሪ አጋጣሚዎችን አልፌያለሁ፡፡
“ሀ በሉ” የተሰኘውን ፊልም ከጓደኛህ ቢኒያም ዳና ጋር ፅፋችሁና መሪ ተዋናይ ሆናችሁ ሠርታችኋል፡፡ ሙዚቃ በውስጣችሁ ስላለ ነው ታሪኩን ከአይዶል ውድድር ጋር ያያያዛችሁት?
ታሪኩን እውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሠረተ ብንለውም ሊያዋጣ ይችላል፡፡ ማንኛውም አይዶል ተወዳዳሪ ብትመለከቺ፣ በዚህ ሂደት ያለፈ ይመስለኛል፡፡ እናም የውድድሩ ሂደት እኛ ፊት ለፊት እንደምንመለከተው አይደለም፡፡ ከጀርባው ስንመለከተው ብዙ ታሪክ አለው፡፡ አይዶል ሊወዳደሩ መጥተው በርካታ ውጣ ውረዶችን ያለፉ፣ “የመጣሁበት አካባቢ ምን ይለኛል” በሚል ሳይመለሱ በዚያው የቀን ስራ፣ የሆቴል አስተናጋጅ እየሆኑ የቀሩ ሞልተዋል፡፡ ወንዱም ዘበኛ የሆነበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡ “ሀ በሉ” ፊልም ላይም የኤጌናና የኦሊሴ ታሪክ ይህን ነው የሚያሳየን፡፡ የሰራነው በአካባቢው የቋንቋ ዘይቤ ነው፤ የተሰራውም የተመረቀውም እዚሁ ሀዋሳ ውስጥ ነው፡፡ እነዚህ ገፀ ባህሪያት አገራቸው ላይ ያየሽው ስኬት ላይ የደረሱት ከስንት ልፋትና መማቀቅ በኋላ ነው፡፡ እና ሙዚቃ ውስጥ ስለሆንን ይህንን እናውቀዋለን፤ ለዚህ ነው የፃፍነው፡፡
ከቢኒያም ጋር ለመስራት እንዴት አሰብክ?
መጀመሪያ ፊልም አልነበረም፡፡ አጫጭር ስታንዳፕ ኮሜዲዎች ነበሩ፡፡ 16 ያህል ቀልዶችን ዳይሬክተሩ ዘታሪያን ጋር ይዤ ሄድኩኝ፡፡ ዘታሪያን የፊልሙ ዳይሬክተር ነው፤ በኋላ ቢኒ ሀሳቡን እንዲያካፍለን አደረግን፡፡ እያንዳንዱን ቀልድ ፊልም ሊያደርግ የሚችል ነፍስ ዘታሪያን ዘራበት፡፡ ከ16ቱ ቀልዶች ታሪክ ሊሆኑ የሚችሉትን መረጥን፡፡ ከነዚህም ውስጥ “አይዶል” የሚለው ቀልድ አንዱ ሆነ፡፡ ሌላው “ስጋ በል ስኩል” የሚለውም ቀልድ ልኳንዳ ቤቱ ላይ ያለውን ክፍል ሸፈነልን፡፡
በዚህ መልኩ ፊልሙ በፕሮፋዩሠርና ተዋናይ ሻሸሞ ዱካሌ በሻና ፊልም ፕሮዳክሽን አማካኝነት ለዚህ በቃ፡፡ በሲዳማ ባህል አዳራሽም ተመረቀ፡፡
በሙዚቃውም ሆነ በፊልሙ ወደፊት ምን አስበሀል?
በነገራችን ላይ ሁለተኛ ፊልሜን ጨርሻለሁ፡፡ “የአይን አባት” የተሰኘ ፊልም ፅፌ ጨርሻለሁ፡፡ ይህ ፊልም ከሙዚቃ ህይወቴም ጋር ይገናኛል፡፡ የ “ሀ በሉ” ፊልም ዳይሬክተር ዘታሪያን ፊልሙን ገምግሞታል፡፡ የተሻለ የታሪክ አወቃቀርና ይዘት እንዳለውም ነግሮኛል፡፡ ወደፊት የምናየው ይሆናል፡
ብዙ ሰው የሙዚቃም ይሁን የፊልም ስራ ተሰጥኦ አለኝ ብሎ ሲያስብ ቀጥታ የሚመጣው ወደ አዲስ አበባ ነው፡፡ እናንተ እዚሁ የተወለዳችሁበት ቦታ ስትሰሩ ገንዘብ ታወጣላችሁና ባያዋጣንስ ብላችሁ አልፈራችሁም?
ይህን ጥያቄ ሸራተንም በተጋበዝኩበት ጊዜ ተጠይቄ ነበር፤ የሚገርመው መስመር የሚጀምረው ከነጥብ ነው አይደለ? እኔ ከነጥብ ጀምሬ ሸራተን ውስጥ በርካቶችን ማሳቅ ችያለሁ፡፡ ፍፁም የራሴ ፈጠራ የሆኑ ፈጠራዎችን ይዤ ማለቴ ነው፡፡ ሸራተን ለመጋበዝ የበቃሁት ግን እዚሁ ሀዋሳ ጀምሬ በሠራሁት ስራ ነው፡፡ ይሳቃል ኢንተርቴይንመንት እኔን፣ ቢኒያምንና ቤሾን ጋብዞን ባገኘሁት አጋጣሚ፣ የእኔና የቢኒን ቁርኝት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ እንደሆንን አድርጌ አስተዋውቄያለሁ፡፡ ምን ለማለት ፈልጌ ነው… የትውልድ አካባቢያችን ላይ ጀምረን ነው ወደ ዋና ከተማው እየተጋበዝን ያለነው፡፡ እዚህ ሀዋሳም ምቹ የኪነ-ጥበብ እድሎች እየተፈጠሩ ስለሆነ ብዙ መስራት እንችላለን፡፡ አሁን ለምሳሌ ሻና ፊልም ፕሮዳክሽን ተከፈተ፤ ብዙ እድሎችን እያመቻቸልን ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ሻሸሞ ዱካሌን አመሰግነዋለሁ፡፡ ከዚህ ባለፈ አዲስ አበባም መጥተን ለመስራት የሚያግደን የለም፡፡ በጣም የምወደውና የማደንቀው ገጣሚና ደራሲ በእውቀቱ ስዩም በጋዝ ላይት የሰጠኝ አስተያየት ወደፊት በርካታ እድሎች ከፊት ለፊቴ እንዳለ የሚያመላክት ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ የትም ሆነሽ ጥሩ ከሰራሽ ስራሽ ራሱ ወደ ዋና ከተማው ይስብሻል፡፡ ይሄ ነው፡፡
በክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ውስጥ ትሰራ ነበር ልበል?
ትክክል ነው የባህል አምባሳደር፣ የመድረክ መሪ እና የግጥምና ዜማ ኤክስፐርት ሆኜ እሰራ ነበር፡፡ አሁን ግን በግሌ የኮሜዲውንም የሙዚቃውንም የፊልሙንም ስራ ለመስራት በገዛ ፈቃዴ ስራዬን ለቅቄ በግሌ እየተንቀሳቀስኩኝ እገኛለሁ፡፡
በመጨረሻ የምትለው ካለ…
የአይን አባት የተሠኘው ፊልሜን ከሠራሁ በኋላ አዲስ አበባ የመግባት ሀሳብ አለኝ፡፡ አንድም የመንግስት ስራዬን የለቀቅኩት በዚህ ምክንያት ነው፡፡ አዲስ አበባ ከመግባቴ በፊት “ምን ይዤ ልግባ” በሚለው መሰረት የቤት ስራዬ ላይ እየሰራሁ ነው፡፡ አዲስ አበባ ብዙ ሙዚቀኞች፣ ብዙ ኮሚዲያኖች፣ ብዙ የፊልም ፀሀፍት እና ተዋንያን ያሉባት ከተማ ናት፡፡ እኔም ተፎካካሪ ሆኜ መግባት አለብኝ እነዛን ስራዎቼን ከወዲሁ እየሰራሁ ነው እልሻለሁ፡፡ በዚህ ሁሉ ስራዬ አብረውኝ የሚሠሩትን አመሠግናለሁ፡፡

 

Published in ጥበብ
Page 8 of 17