ከ10 ዓመት በላይ እስር ሊያስቀጣ ይችላል 

በአየር ጤና ሁለተኛና መሰናዶ ት/ቤት ለ11 የዘጠነኛ ክፍል ተማሪዎች ጉቦ እየተቀበለ የፈተና ውጤት በመጨመር ከክፍል ወደ ክፍል እንዲዘዋወሩ አድርጓል የተባለው የባዮሎጂ መምህሩ አቶ ፈቃዱ ቢጀጋ በሙስና ወንጀል ክስ ተመሠረተበት፡፡
የፌደራሉ የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አቃቤ ህግ፣ የክስ ዝርዝር እንደሚያስረዳው፤ በመምህሩ ላይ ሁለት ክሶች የቀረቡበት ሲሆን በአንደኛው ክስ በ2005 የትምህርት አመት የ9ኛC ክፍል የክፍል ሃላፊ ሆኖ የተመደበበትን ስልጣን ያለአግባብ በመጠቀም፣ ከሰኔ 28 እስከ ሐምሌ 7 ቀን 2005 ዓ.ም ድረስ ለአስራ አንድ ተማሪዎች ዘጠኝ የሚደርሱ የትምህርት አይነቶች ላይ ለእያንዳንዱ የትምህርት አይነት መምህራን ሳያውቁ እስከ 91 ነጥብ በመጨመር ከክፍል ወደ ክፍል ማለፍ የማይገባቸው ተማሪዎች እንዲያልፉ ለማድረግ በማሰብ፣ ከስልጣኑ በላይ በሆነ አሠራር በመንግስት የትምህርት ጥራት ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረሱ፣ በፈፀመው በስልጣን ያለአግባብ መጠቀም የሙስና ወንጀል እንደተከሰሰ ተመልክቷል፡፡
በሁለተኛነት በቀረበው ክስ ላይም ሃላፊነቱን ያለአግባብ በመጠቀም የግል ተበዳይ የሆነ አንድ ተማሪ ካርድ እንዲሰጠው ሲጠይቀው “ውጤትህ የተሟላ አይደለም፤ የተሟላ ውጤትህን የያዘ ካርድህን እንድሰጥህ ከፈለግህ ገንዘብ አምጣ” በማለት ጠይቆ፣ ሐምሌ 8 ቀን 2005 ዓ.ም ከጠዋቱ 3 ሰአት ሲሆን በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4፣ አንድ ግሮሰሪ ውስጥ ከግል ተበዳይ 200 ብር ተቀብሎ “ካርድህን እልክልሃለሁ፤ ገንዘብ ግን ስለሚያንስ ትጨምራለህ” በማለት በነጋታው ከምሽቱ 12 ሰዓት ሲሆን ተጨማሪ 150 ብር ከዚሁ ተበዳይ ሲቀበል እጅ ከፍንጅ በመያዙ በሙስና ጉቦ በመቀበል ወንጀል ተከሷል፡፡
ክሱ እንደደረሰው ለፍ/ቤቱ ያረጋገጠው ተከሳሽም፣ በችሎቱ በተገኙና ሊረዱት በፈለጉ ጠበቆች አማካይነት የተከሰሰበት የህግ አንቀጽ ዋስትና የማያስከለክል በመሆኑ፣ “ፍ/ቤቱ ጉዳዬን በዋስ ሆኜ እንድከታተል ይፍቀድልኝ” ሲል የጠየቀ ሲሆን አቃቤ ህግም በዋስትና ጥያቄው ላይ ተቃውሞ እንደሌለው አመልክቷል፡፡
ይሁን እንጂ ተከሳሹ ከ10 አመት በላይ በሚያስቀጣ ወንጀል የተከሰሰ በመሆኑ የዋስትና ጥያቄውን ባለመቀበል፣ መዝገቡን ለነሐሴ 3 ቀን 2005 ዓ.ም ቀጥሯል፡፡

Published in ዜና

ችግር ፈጥረዋል የተባሉ 10 ያህል ሰዎች ተይዘዋል
በአዲስ አበባ ፍልውሃ አካባቢ በሚገኘው ቶፊቅ መስጊድ ትናንት ተቃውሞ እንደሚካሄድ ቀድሞ በመነገሩ፣ በአካባቢው በርካታ ፖሊሶችና አድማ በታኞች ከረፋዱ አንስቶ የተሰማሩ ሲሆን፣ ቀትር ላይ የተቃውሞ ድምፆች ሲስተጋቡና የተወሰኑ ወጣቶች በፖሊስ ተይዘው ሲወሰዱ ታይቷል፡፡ 
በኢንተርኔት አማካኝነት “አንድነታችን ይቀጥል” በሚል በተላለፈው የተቃውሞ ጥሪ፣ በርካታ ሰዎች ወደ ቶፊቅ መስጊድ መምጣታቸው ታውቋል፡፡
በሌላ በኩል በመስጊዱ እንዲካሄድ የታሰበውን ተቃውሞ በማስቀረት በኢድ (በረመዳን ፆም ፍቺ) ዕለት እንዲካሄድ ጥሪ የሚያስተላልፍ ሌላ መልእክት ትናንት ማለዳ እንደተሰራጨ ተነግሯል።
ከመስጊዱ ውስጥና ዙሪያ በተጨማሪ በርካታ ህዝብ በሦስት አቅጣጫ የተሰበሰበ ሲሆን፤ ፖሊሶች የአንደኛው አቅጣጫ ወደ ሌላኛው እንዳይሄድ በየመሃሉ ተሰልፈው ሲቆጣጠሩ ታይቷል፡፡
በእለቱ ከፍተኛ የተቃውሞ ድምጽ ሲስተጋባ የነበረው መስጊዱ በር አጠገብ ነው፡፡ ከበር አጠገብ ከፍታ ቦታ ላይ ከቆሙት ወጣቶች መሃል አንዱ ወጣት፣ ሲቪል በለበሱ ሁለት የፀጥታ ሃይል አባላት ተይዞ ሲወሰድ፣ እዚያው አካባቢ የነበሩ በርካታ ሰዎች ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ በጩኸትና ጣታቸውን ወደ ላይ በማውጣት ተቃውሟቸውን ገልፀዋል፡፡ በሦስቱ የመኪና መንገድ አቅጣጫዎች በርቀት እንዲቆሙ የተደረጉ ሌሎች በርካታ ሰዎችም ተቃውሞውን መላልሰው አስተጋብተዋል፡፡ የልጁን መያዝ በመቃወም የተከራከሩ ሰዎችም እንዲሁ በፀጥታ ሃይል አባላት ተይዘው ታይተዋል፡፡ አስር የሚሆኑ ሰዎች በፖሊስ መኪና የተወሰዱ ሲሆን፤ ይህንንም ተከትሎ ብዙ ሰዎች በተቃውሞ ድምፃቸውን አሰምተዋል፡፡
በቶፊቅ መስጊድ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ የነበሩ ሰዎች ከስግደት በኋላ፣ ተቃውሞውን ለመቀጠል በያሉበት በመቆም ሲጠባበቁ የነበሩ ቢሆንም፣ ከአካባቢው በፍጥነት እንዲሄዱ በፖሊሶች እየተነገራቸው እንዲበተኑ ተደርጓል፡፡
ተቃውሞውን ለመቆጣጠር የከተማ እና የፌደራል ፖሊስ አባላት እንዲሁም አድማ በታኞች በብዛት ከመሰማራታቸውም በተጨማሪ በመስጊዱ ዙሪያ የሚገኙ ብዙዎቹ የንግድ ቤቶች በስጋት ተዘጋግተው ነበር፡፡ ባለፈው ሳምንት አርብ ብዙ ህዝብ በተገኘበት በበኒ መስጊድ እንዲሁም ከዚያ በፊት በነበሩ ሳምንታት በአንዋር መስጊድ ተቃውሞ መካሄዱ ይታወሳል፡፡

Published in ዜና

200ሚ. ብር የወጣበት ሆቴል በአዲስ አመት ይመረቃል

የዓለምና የኦሎምፒክ የ5 እና የ10ሺ ሜትር ሩጫ ሪከርድ ባለቤት ቀነኒሳ በቀለ፤ በ200 ሚሊዮን ብር ያስገነባው ባለ 4 ኮከብ ዘመናዊ ሆቴል ነገ አገልግሎት ይጀምራል፡፡ 
ከቦሌ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት የተሰራውና በጀግናው አትሌት ስም የተሰየመው ቀነኒሳ ሆቴል፤ ባለ 7 ፎቅ ሲሆን 51 የመኝታ ክፍሎች እንዳሉት ታውቋል፡፡
ሆቴሉ፣ ሱዊት፣ ጥንድ፣ ሲንግል፣ የቤተሰብና ለአካል ጉዳተኞች ታስቦ የተሰሩ ክፍሎች ሲኖሩት፣ ሱት የሚባሉትን 10 ክፍሎች ጨምሮ 22 ክፍሎች ጃኩዚ እንዳላቸው የሆቴሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሪት ሮማን ታፈሰወርቅ ገልፀዋል፡፡
ሥራ አስኪያጇ አክለውም፣ ሆቴሉ በአሁኑ ወቅት ለመቶ ሠራተኞች የሥራ ዕድል የፈጠረ መሆኑን ጠቅሰው ሠራተኞቹ ቀደም ሲልም በሆቴል ሙያ እውቀትና ልምድ ቢኖራቸውም የአንድ ወር ሥልጠና እንደተሰጣቸውና ሥልጠናው ወደፊትም እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
በቂ የመኪና ማቆሚያ ስፍራ መኖሩ ልዩ ያደርገናል ያሉት ወ/ት ሮማን፤ የደንበኞቻቸውን ምቾት ለመጠበቅ፣ ለክፍሎቹ ብቻ ሳይሆን ለሆቴሉ በአጠቃላይ የአየር ሙቀትና ቅዝቃዜ መቆጣጠሪያ መሳሪያ (ኤሲ) መገጠሙን ገልፀዋል፡፡ ከሁሉም በላይ የእንግዶቻቸውን ደህንነት ማረጋገጥ አስፈላጊ በመሆኑ፣ ሁሉም ክፍሎች ጭስ ጠቋሚ (አነፍናፊ) መሳሪያ፣ የእሳትና ድንገተኛ አደጋ መከላከያ ሲስተም (ማምለጫ ደረጃዎች)፣ በየቦታው የውሃ መርጫና ጠቋሚ ካሜራዎች መገጠማቸውን አስረድተዋል፡፡
የድምፅ ብክለትን ለመከላከል በሮቹና መስኮቶቹ ድምፅ የማያስተላልፉ (ሳውንድ ፕሩፍ) መሆናቸውንና ዕቃዎቹ በሙሉ የባለ 5 ኮከብ ሆቴል መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
ሰፊና ዘመናዊ ሎቢ ባር፣ ካፊቴሪያ፣ የባህላዊና ዘመናዊ ምግቦች ሬስቶራንት፣ ቪአይፒ ላውንጅ፣ እንግዳው በንፁህ አየር እየተዝናና ፒዛ መብላት፣ ቢራና ድራፍት መጠጣት እፈልጋለሁ ቢል ምቹ (ኦፕን አየር) ስፍራ ተዘጋጅቷል፡፡
ሆቴሉ፣ ሁለት የእንግዶችና አንድ የሠራተኞች መጠቀሚያ አሳንሰር (ሊፍት) ሲኖረው፣ ፈጣን ብሮድ ባንድ ኢንተርኔትና ሽቦ አልባ (ዋየርለስ)፣ ሳውና ባዝ፣ ስቲም ባዝ፣ ጃኩዚ፣ ሁለገብ ጂምናዚየም፣ ኤሌክትሮኒክስ ገንዘብ መቀበያ ካርድና የተለያዩ የንግድ ማዕከላት ሲኖሩ 24 ሰዓት አገልግሎት እንደሚሰጥ ታውቋል፡፡ ወ/ሪት ሮማን ታፈሰወርቅ፤ ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በሆቴል ማኔጅመንት የመጀመርያ ዲግሪ ሲኖራቸው፣ ለሁለተኛ (ማስተርስ) ዲግሪያቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ማርኬቲንግ ማኔጅመንት እየተማሩ ናቸው፡፡

Published in ዜና

ሙሉጌታ ውለታው፤ የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ
ሰማያዊ ፓርቲ፤ ግንቦት ሰባት እና አክራሪዎች ህገመንግስቱ ከሚፈቅደው ውጪ ሀይማኖትና ፖለቲካን በማደባለቅ ለመስራት ጋብቻ ፈፅመዋል ሲሉ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሙሉጌታ ውለታው ተቹ፡፡
ከነሐሴ 21-23 ቀን 2005 ዓ.ም በአገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደውን የሀይማኖት ኮንፈረንስ በማስመልከት በአዳማ ከተማ ለሚዲያ እና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች እየተሰጠ ባለው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ላይ የተገኙት ሚኒስትር ዴኤታው፤ “መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ ገባ ማለት በእሳት ተጫወተ ማለት ነው፤ አሁንም ሆነ ወደፊት ጣልቃ አይገባም” ብለዋል፡፡
ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሙስሊሙ ህብረተሰብ የሀይማኖት ነፃነት አልተከበረም በሚል ተቃውሞ ማሰማታቸው እንዴት ይታያል? በሚል የተጠየቁት ሚኒስትር ዴኤታው፤ “በክርስቲያንም ሆነ በሙስሊሙ ያልተመለሰ የሀይማኖት ጥያቄ የለም፤ ያልተመለሰም ካለ የሰማያዊ ፓርቲ እና የግንቦት ሰባት ጥያቄ ነው” ያሉት ሚንስትር ዴኤታው፤ የነዚህ አካላት ጥያቄም ሀይማኖትን ሽፋን ያደረገ የፖለቲካ ጥያቄ እንጂ የሀይማኖት አለመሆኑ ግልፅ ነው ብለዋል፡፡
“በዚህ ጉዳይ ላይ አጥፊና አፍራሽ ጉዳዮችን አብሮ ለመፈፀም ሰማያዊ ፓርቲ፣ ግንቦት ሰባት እና አክራሪዎች ጋብቻ ፈጽመዋል፤ ጋብቻቸውም ግልጽ ያልሆነ እና “ኦድ ኬሚስትሪ” (ያልተለመደ ቁርኝት) ነው” ብለዋል፡፡ መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ እየገባ ነው በሚል የሚነሳውን ወቀሳ በተመለከተ ሲናገሩም፤ መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ ገባ ማለት በእሳት ተጫወተ ማለት እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ሙሉጌታ፤ አክራሪዎች በሚያነሱት ረብሻ ሰላማዊ ህዝብ እንዳይበጠበጥ መንግስት ሠላም የማስከበሩን ሃላፊነትን ሲወጣ ጣልቃ ገባ ማለት አግባብ አለመሆኑንና አንዲትም ኢንች ጣልቃ እንዳልገባና ወደፊትም እንደማይገባ ገልፀዋል፡፡
አክራሪዎች ጥቂት ናቸው ከተባለ ለምን ጉዳዩ እንዲህ አንገብጋቢ ሆነ ተብሎ ለተነሳው ጥያቄም “ጉዳዩ አለምአቀፍ ስጋት ነው፤ ችላ ከተባለ የዕንቁላሉ ስርቆት ወደ በሬ ስርቆትነት ስለሚሸጋገር በእንጭጩ መቀጨት አለበት”ያሉት ሚንስትር ዴኤታው፤ መንግስት እየሰራ ያለው በእንቁላሉ ጊዜ በቀጣሽኝ አይነት እርምጃ እንደሆነም አስምረውበታል፡፡
የሼሁን ግድያ በተመለከተ፤ ተጠርጣሪዎች ፍ/ቤት ቀርበው ሳይፈረድባቸው በመንግስት መገናኛ ብዙሃን አሸባሪ መባላቸውን በተመለከተ ሲመልሱ፤ “መገናኛ ብዙሃኑ ተጠርጣሪ እንጂ አሸባሪ አላሉም” ሲሉ በማለት አስተባብለዋል፡፡
በእስር ላይ የሚገኙት “የሙስሊሞች ችግር መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ” አባላት ቀደም ሲል ከመንግስት ጋር ሲደራደሩ የነበሩ ከመሆኑ አንፃር፣ እነሱን “አሸባሪ” ብሎ ማሰሩ ጉዳዩን አክርሮታል ይባላል በሚል ስለ ጉዳይ የተጠየቁት ሚኒስትር ዴኤታው፤ “የሀይማኖት ጥያቄ አንስቶ የታሰረ የለም፤ ያጠፉትም ቢሆኑ ሁሉም አልታሰሩም” ካሉ በኋላ በተመረጠ አካኋን ከሀይማኖት ውጪ ችግር ሲፈጥሩ በፖሊስ የተያዙ ጥቂት ሰዎች ብቻ መታሰራቸውን እና ስለጥፋተኝነታቸውም ፖሊስ ተጨባጭ ማስረጃ እንዳለው አብራርተዋል፡፡
“የሀይማኖቶች በሰላም አብሮ የመኖር እሴትን በማጎልበት እና ህገመንግስታዊ ድንጋጌዎችን በማክበር የሀገራችንን ህዳሴ ጉዞ ለማሳካት እንረባረባለን” በሚል መሪ ቃል ከነሀሴ 21-23 ቀን 2005 ዓ.ም ድረስ ለሚደረገው አገር አቀፍ የሀይማኖት ኮንፈረንስ፣ ጋዜጠኞች ሊኖራቸው በሚችለው ሚና ዙሪያ የተሰጠው ስልጠና ትላንት አመሻሽ ላይ ተጠናቋል፡፡

Published in ዜና

ተቀማጭ ገንዘቡ ወደ 3.5 ቢሊዮን ብር አደገ
ከአንድ ሚሊዮን በላይ ደንበኞች አፍርቷል
አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ ዘንድሮ በባንኩ ታሪክ ከፍተኛ የተባለ የ639 ሚሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ፡፡ በውጭ ኦዲተሮች መረጋገጥ ይቀረዋል የተባለው የትርፍ መጠን ከአምናው ጋር ሲነፃፀር በ180.6 ሚሊዮን ብር ወይም በ18 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተገልጿል፡፡
በ115 ቅርንጫፎቹ ከአንድ ሚሊዮን ለሚበልጡ ደንበኞቹ ዘመናዊና ቀልጣፋ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን የገለፀው ባንኩ፤ በዚህ አመት ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች 2.2 ቢሊዮን ብር ብድር መስጠቱንና እስከ አሁን የሰጠው ብድርም ከ7.7 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን አስታውቋል፡፡
ዘንድሮ የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ ወደ 3.5 ቢሊዮን ያደገ ሲሆን፣ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ37 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ የባንኩ ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘብም ባለፈው ሰኔ ወር መጨረሻ 13.1 ቢሊዮን ደርሷል፡፡ በዚህ ዓመት የባንኩ ጠቅላላ ገቢ ከብር 1.4 ቢሊዮን በላይ የደረሰ ሲሆን፣ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ28 በመቶ ወይም የ309 ሚሊዮን ብር ዕድገት ማስመዝገቡ ገልጿል፡፡
የባንኩ የተከፈለ ካፒታል ከ1.2ሚሊዮን ብር በላይ የደረሰ ሲሆን፣ አምና ከነበረው 912ሺህ ብር ጋር ሲነፃፀር የ27 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ የባንኩ ጠቅላላ ባለ አክሲዮኖች በወሰኑት መሠረት በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት የተከፈለ ካፒታሉን ወደ 1.5 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ታቅዷል፡፡
የባንኩን የቴክኖሎጂ አቅም በማሳደግ ረገድ ማይሲስ ከተባለ የእንግሊዝ ድርጅት ጋር የ3.5 ሚሊዮን ዶላር የቴክኖሎጂ ማስፋፊያ (ኮር ባንኪንግ) ሥራዎች በማከናወን ላይ ሲሆን፣ ከአይቢ ኤም ድርጅት ጋር የ2.5 ሚሊዮን ዶላር የሶፍትዌር፣ የሃርድዌርና ተዛማጅ ግዢዎችና ሥልጠናዎች ስምምነት ላይ መድረሱን አስታውቋል፡፡
ዘመናዊ የካርድ ቴክኖሎጂን በተመለከተ፣ አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ ንብ ኢንተርናሽናል ባንክና ሕብረት ባንክ በጋራ ባቋቋሙት ፕሪይመር ስዊች ሶሉሽን አማካይነት “አዋሽ ካርድ” ያዘጋጀ ሲሆን በዚህ ካርድ በሦስቱም ባንኮች ባሉ የክፍያ ተርሚናሎች (ኤቲኤም) በመጠቀም ደንበኞች ጊዜአቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ማስቻሉን አስታውቋል፡፡

Published in ዜና

ዘንድሮ ብቻ 41 ሰዎች በጎርፍ ተወስደው ሞተዋል
በልደታ ቤተክርስቲያን አካባቢ በሚገኝ ወንዝ ውስጥ ገብተው በጐርፍ የተወሰዱት ሴት አስከሬን እስካሁን አልተገኘም፡፡ የልደታ ቤ/ክ አካባቢ ነዋሪ የሆኑት የ69 ዓመቷ አዛውንት ፀዳለ አለባቸው፤ ልደታ ቤተክርስቲያን ቆይተው ሲመለሱ የጫማቸውን ጭቃ ለማጠብ ወደ ወንዙ ሲጠጉ የረገጡት መሬት ተደርምሶ ወንዝ ውስጥ በመግባታቸው ደራሽ ጐርፉ ይዟቸው እንደሄደ የአይን እማኞች ተናግረዋል፡፡ 

በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የእሳትና ድንገተኛ አደጋ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ በበኩላቸው፤ የወ/ሮ ፀዳለ አስከሬን ሊገኝ ያልቻለው ቤተሰብ በዕለቱ ባለማመልከቱ መሆኑን ገልፀው፣ ብዙ ጊዜ በጎርፍ የሚወሰዱ ሰዎች አስክሬን በሌላ አካባቢ ጎርፉ ሲተፋቸው እንደሚገኝና የወ/ሮ ፀዳለን አስክሬንም ለማግኘት ወንዙ የሚሄድበትን አቅጣጫ እየተከተሉ ፍለጋቸውን እያከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ጎርፉ ራቅ ያለ አካባቢ ወስዶ ከጣላቸው በኋላ ቶሎ መገኘት ካልቻሉ አስከሬኑ በአውሬ የመበላት እድል እንደሚገጥመው ገልፀው፤ አብዛኛውን ጊዜ ግን የሚጠፋ አስክሬን እንደማይኖር ተናግረዋል፡፡
ዘንድሮ በጎርፍ አደጋ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች 41መሆናቸውን የገለፁት ባለሙያው፤ ባለፈው ዓመት 34 ሰዎች በጐርፍ ተወስደው መሞታቸውን ተናግረዋል፡፡

Published in ዜና

“እናቴ የኤች አይቪ ቫይረስ በደሟ ውስጥ ይገኛል፤ እኔና እህቴ ከእናታችን ውጪ ማንም የለንም፡፡ ሰባት መፅሀፌን አቃጥለውብኛል፤ በዚህ የተነሳ በትምህርቴ ውጤት ላመጣ አልቻልኩም፣ ከምማርበት ይልቅ ከት/ቤት የምቀርበት ቀን ይበልጣል፣ እናቴ ቀበሌው ቤት ይፈልግልሻል ተብላ ነበር፤ በኋላ ተቀንሰሻል አሏት፡፡ ለምን ብላ ስትጠይቅ፣ አንቺ የኤች አይቪ ቫይረስ በደምሽ ውስጥ የለም፣ ውሸትሽን ነው ተባለች፡፡ እናንተ ግን እናቴን ሂዱና እይዋት፣ ፎቶም አንሷት፣ የምትወስደውንም መድሃኒት ተመልከቱ፡፡ ”ይህ የ12 ዓመቷ ታዳጊ ቃልኪዳን ተመስገን በእንባ ጎርፍ የታጀበ ንግግር ነው፡፡ ቃልኪዳን በጆኔፍ ት/ቤት የ6ኛ ክፍል ተማሪ ናት፡፡ አራት ኪሎ ቤተመንግስቱ ስር ባለውና በአረንጓዴና ቢጫ ቀለም ቅብ በታጠረው የቆርቆሮ አጥር ስር ከእናቷና ከታናሽ እህቷ ጋር በላስቲክ ቤት ውስጥ የወደቀባትን ሀላፊነት ለመወጣት የምትቃትት ህፃን ናት፡፡ አቶ ጀማል ሁሴን ለመልሶ ማልማት በፈረሰው የአራት ኪሎ መንደር ለ23 ዓመታት እንደኖሩ ይናገራሉ፡፡ ከዚህ በፊት ትንሽ ብር እየከፈሉ ዘመድ ቤት በጥገኝነት ይኖሩ ነበር፡፡

ከዚያም ልጅ ወልደው እና አካባቢውን መስለው በሰላም ይኖሩ እንደነበር አጫውተውኛል፡፡ “ሙዘይን ጀማል የተባለ የ18 ዓመት ልጅ አለኝ፡፡ በችግር ምክንያት ትምህርቱን ባያቋርጥ ኖሮ አሁን ዩኒቨርስቲ መግቢያው ነበር” የሚሉት አቶ ጀማል፤ አሁን ግን የሚረዳው በማግኘቱ ያቋረጠውን ትምህርት መጀመሩን ይናገራሉ፡፡ ይሁን እንጂ አቶ ጀማልና ቀሪ ቤተሰቦቻቸው ያለ ስራ ያለመጠለያ፣ ያለመብራትና ውሀ ሙጃ ሳር በከበበው የአራት ኪሎ ሜዳ ላይ ከነልጆቻቸው ስድስት ሆነው በወጠሩት ላስቲክ ቤት ውስጥ የመከራ ኑሮ እየገፉ ይገኛሉ። አሊ ጀማል የተባለው ልጃቸው የሚለብሰውና የሚማርበት ቁሳቁስ እንዲሁም ምግብ በማጣቱ ትምህርቱን እንዳቋረጠም በእንባ ይናገራሉ፡፡ የ62 ዓመቱ ስመኝ ላቀውም ከ15 ዓመት በፊት ሸራተን ፊት ለፊት በነበረውና አሁን ለመልሶ ማልማት በፈረሰው መንደር ውስጥ በጥገኝነት ይኖሩ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ቀበሌው ላለፉት 15 ዓመታት በጥገኝነት መኖራቸውን እንደሚያውቅ በተደጋጋሚ ቤት እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውና አሁን ግን ጭራሽ ቤቶች ሲፈርሱና ያስጠጓቸው ሰዎች ቤት አግኝተው ሲሄዱ እነሱ ሜዳ ላይ መውደቃቸውን ይገልፃሉ። በዚህ ኑሮ አራት አመት እንዳስቆጠሩ የሚናገሩት እኚህ አባት፤ ልጆቻቸውን ወደ ትውልድ አገራቸው ሀረር ልከው በየዘመድ ቤት እንዳስጠጓቸውም አውግተውኛል፡፡ “አሁን ያለነው ያለ ውሀ፣ ያለ ምግብና መጠለያ እዚህ ወንዝ ውስጥ ነው፡፡

ማታ ማታ ጅቦች እየመጡ በላያችን ላይ ሲሮጡብን ያድራሉ፤ ህፃናትን እንዳይበሉብን በርካታ ውሾችን አሠማርተን እኛም ተራ በተራ እየተከላከልን በስቃይ እንኖራለን” በማለትም ጨምረው ይናገራሉ፡፡ እንደ አቶ ስመኝ ገለፃ፤ ችግራቸው ይሄ ብቻ አይደለም። ቦታው በቆርቆሮ ከመታጠሩም በተጨማሪ የበቀለበት ረጃጅም ሙጃ ለሌቦች መደበቂያ በመሆኑ ሌቦች ሰርቀው አጥር ውስጥ ሲገቡ ፖሊሶች መጥተው ሌቦቹን አውጡ በማለት እንግልት እንደሚፈፅሙባቸው በምሬት ይናገራሉ፡፡ አቶ ምትኩ ገብሬ የ75 ዓመት አዛውንት ናቸው። እርጅናና ጉስቁል የተጫናቸው አቶ ምትኩ፤ ጅማ ውስጥ ተወልደው ማደጋቸውን አጫውተውኛል። በደርግ ጊዜ ኢህአፓ እየተባለ ሰው ሲባረር በኢህአፓነት ተጠርጥረው ያለ ምንም ማስረጃ መታሠራቸውንና ከእስር ቤት አምልጠው ሱዳን መግባታቸውን ይናገራሉ፡፡ ከሱዳን ተመልሰው አዲስ አበባ መኖር የጀመሩት እዚሁ አራት ኪሎ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ምትኩ፤ ላለፉት 19 ዓመታት ሠው አስጠግቷቸው ይኖሩ እንደነበርም ያብራራሉ፡፡ ገና ከሱዳን እንደመጡ ጉልበታቸውም ሆነ ጤንነታቸው ደህና ስለነበር አነስተኛ ቤት ተከራይተውና ያገኙትን እየሠሩ ይኖሩ እንደነበር ገልፀው፤ እድሜና የጤና ችግር እየተጫናቸው ሲሄድ ያከራየቻቸው ሴት “ለፈጣሪ ይሆነኛል” በሚል ኪራዩን ትተው እንዳስጠጓቸው፣ አሁን ግን እዚህ ሜዳ ላይ መውደቃቸውን የሞጨሞጩ አይኖቻቸው እንባ እየተሞሉ አጫውተውኛል፡፡ እኚህ አባት አሁን ጤናቸው ተቃውሷል፡፡ አይናቸውንም እንደሚጋርዳቸው ይናገራሉ፡፡ አቶ ምትኩ በተለይም ኑሯቸውን የከፋ ያደረገው የአስም በሽታቸው ነው፡፡ ቅዝቃዜው ለአስም በሽታቸው መባባስ ምክንያት ሆኖ መተንፈስ እየተሳናቸው ነው ያነጋገሩኝ፡፡ “እኔ የምለብሰው ልብስ በቀበሌ ሹማምንቶች ተወስዷል፤ አሁን ገላዬ ላይ ጣል ያደረግኩትን አሮጌ ጨርቅ ለነፍሴ ያለ ነው ጣል ያደረገብኝ፤ ከዚህ በላይ ሞት የለም፣ ተስፋ ቆርጫለሁ” ሽማግሌው ሳግ እየተናነቃቸው ሀሳባቸውን ለማቋረጥ ተገድደዋል፡፡ አቶ ቱሉ በየነ ይባላሉ፡፡ ትውልዳቸው ምንጃር ነው፡፡

ከትውልድ ቀያቸው መቼ እንደወጡ ወሩንና ዓመቱን ባያውቁውም ከምንጃር ከወጡ በኋላ ደብረ ዘይት ለተወሠኑ ዓመታት መኖራቸውን ነግረውኛል፡፡ የደብረዘይት ኑሯቸው ስላልተመቻቸ የዛሬ 17 ዓመት አራት ኪሎ መጥተው መኖር ጀመሩ፡፡ “አሮጌው ቄራ አካባቢ ወ/ሮ አስካለ የተባለች ሴት ጋር በጥገኝነት ነው የኖርኩት” የሚሉት አቶ ቱሉ፤ አካል ጉዳተኛም ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ሶስት ልጆቻቸውና ባለቤታቸውን ይዘው በወጠሯት የላስቲክ ቤት ውስጥ አምስት ሆነው ዝናብና ብርድ በላያቸው ላይ እየወረደ ኑሮን ቀጥለዋል፡፡ “ቦታ ተመድቧል በአጭር ጊዜ ውስጥ ሠርተን እናስገባችኋለን ሲሉን ቆይተው፣ ምን አደረጋችሁልን ብለን ስንጠይቅ ለእናንተ የተመደበው በጀት ተቃጥሏል፤ አዲሱን ካቢኔ ጠይቁ አሉን” የሚሉት አቶ ቱሉ፤ ሹም ሽር እየተካሄደ አዳዲስ የወረዳ አስተዳዳሪዎች በመጡ ቁጥር የእነሱ ጉዳይ እየደበዘዘና እየተረሳ ከችግር የሚላቀቁበት ጊዜ እንደናፈቃቸው በምሬት ይናገራሉ፡፡ “ቤት ልንሠራላችሁ ነው ሲሉን እኛ ሌላ ነገር ባይኖረንም በአቅማችን በጉልበታችን እናግዛችሁ እስከማለት ደርሠን ነበር” የሚሉት አቶ ቱሉ፤ እንኳን አዲስ ቤት ሊገቡ ቀርቶ ጭራሽ ወንዝ ውስጥ ላስቲክ ወጥረው የሚኖሩበትን ቤት ከስምንት ጊዜ በላይ በእሳት እንዳጋዩት ይናገራሉ፡፡ “ከሌሊቱ ስምንትና ዘጠኝ ሰዓት እየመጡ ላስቲክ መጠለያችንን ሲያቃጥሉብን ወደ ሬዲዮ ጣቢያዎች ሄደን ብንናገርም ይህን ይፋ ያደረገ እና ጩኸታችንን የሠማ የለም” ትላለች፤ የሁለት ልጆች እናት የሆነችውና ስሟን መጥቀስ ያልፈለገች አንዲት እናት፡፡ “አሁን እዚህ ወንዝ ዳር ከመምጣታችን በፊት በሸራተን ሆቴል በኩል ከጭቃማው ቦታ የሚሻል ጠፈፍ ያለ ቦታ ላይ ነበርን፤ ለአፍሪካ ህብረት 50ኛ የምስረታ በዓል እንግዶች ስለሚመጡ ከዚህ ልቀቁ ተብለን ወንዝ ውስጥ ደበቁን” የሚለው የሁሉም ችግረኞች ድምጽ ጆሮን ይሠቀጥጣል፡፡ አቶ አያሌው ነጋሽ የ53 ዓመት ጐልማሳ ናቸው።

በቤት እጦት ምክንያት ልጆቻቸውን በተለያየ የዘመድ ቤት አስጠግተው፣ ከባለቤታቸው ጋር በላስቲክ ቤታቸው ውስጥ የችግር ኑሮ እየገፉ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ እኚህ ጎልማሳ አራት ኪሎ መኖር ከጀመሩ 18 ዓመታቸው ነው፡፡ አራት ኪሎ ከመምጣታቸው በፊት የነበራቸው ህይወት የውትድርና ነው፡፡ ኢህአዴግ ግንቦት ወር ላይ ሊገባ እርሳቸው መጋቢት ላይ በጦርነቱ ተመትተው ቦርድ ከወጡ በኋላ ወደ አራት ኪሎ እንደመጡ ይናገራሉ። “ቦታው ለልማት ይፈለጋል ተብሎ የአካባቢው ነዋሪ ስብሰባ ሲጠራ እኔም ቀበሌው ውስጥ እንደመኖሬና ተከራይ እንደመሆኔ በስብሰባው ላይ ተካፍዬ ነበር” የሚሉት አቶ አያሌው፤ የግል ይዞታና የቀበሌ ቤት ያላቸው ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ እኛም ረጅም አመት በዚህ አካባቢ የኖርነው ጉዳይ ይታሰብበት የሚል ሀሳብ እንዳነሱም ይናገራሉ፡፡ ይሁን እንጂ ሀላፊዎቹ “ድሮም ተጠግታችሁ ነው የምትኖሩት አሁንም የሚያስጠጋችሁ ፈልጉ” የሚል ከአንድ ሀላፊነት ከሚሰማው ዜጋ የማይጠበቅ ምላሽ ሰጡን ያሉት እኚህ ነዋሪ፤ “እኔ ሜዳ ላይ እንደምወድቅ ያወቅሁትና ተስፋ የቆረጥኩት ያን ጊዜ ነው” ይላሉ። ከላይ የጠቀስነውን የስቃይ ኑሮ በላስቲክ ቤት የሚገፉትን 48 አባዎራዎች ሁኔታ ከርቀት ለመመልከት ከፒያሳ በአቋራጭ በሚጭነው ታክሲ ወደ ካሳንቺስ ሲመጡ አሻግረው ወደ ቤተመንግስቱ ይመልከቱ፡፡ የላስቲክ ቤት “መንደሮችን” ለመቃኘት አመቺው ሥፍራ ይሄ ነው፡፡ እነዚህ ቤት አልባ ዜጎች ትራሳቸው ቤተመንግስቱ ነው፤ ግርጌያቸው ደግሞ ባለ አምስት ኮከቡ ሸራተን አዲስ ሆቴል፡፡ የአገሪቱ አናት የሆነው ቤተመንግስት ስር በኩራዝ መብራት የሚኖሩ ስራ፣ መጠለያ እና የጤና አገልግሎት የማያገኙ ዜጎች “እየኖሩ” ነው፡፡

ጩኸታቸውን ቤተመንግስቱ እንዳይሰማ በቢጫና አረንጓዴ ቀለም ያጌጠው የቆርቀቆሮ አጥር የከለለው ይመስላል፡፡ 48ቱ አባወራዎች እያንዳንዳቸው በአማካይ አምስት ቤተሰብ እንዳላቸው እነዚሁ ችግረኞች ይናገራሉ፡፡ በልመናና በጉልበት ስራ የሚተዳደሩ ናቸው፡፡ ልጆቻቸው የምግብና መጠለያ እንዲሁም የመብራት እጦት ሰለባ በመሆናቸው ትምህርታቸውን አቋርጠዋል፡፡ በርካታ የኤችአይቪኤድስ ታማሚዎች እንዳሉም ሰምተናል። ከነዚህም ውስጥ የህፃን ቃልኪዳን ተመስገን እናት ወ/ሮ መሰረት አንዷ ናት፡፡ ይሄውም ኑሮ ሆኖ የላስቲክ ቤታችንን ከስምንት ጊዜ በላይ አቃጥለውብናል” ይላሉ አቶ ጀማል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን እንደ ዜጋ የመምረጥ መመረጥ መብታቸው ተነፍጎ 48ቱም አባወራዎች የምርጫ ካርድ እንዳይወስዱ መከልከላቸውንም በእንባ እየታጠቡ አጫውተውናል፡፡ ወረዳውም ክ/ከተማውም የአካባቢው ነዋሪ መሆናችንን ያውቃል፤ ግማሾቻችን የቀበሌ መታወቂያ አለን፤ የግማሾቻችን የላስቲክ ቤታችንን ሲያቃጥሉ አብሮ ተቃጥሏል። እኛ እንደዜጋ አንቆጠርም፣ ቅኝ ግዛት ውስጥ ነው ያለነው” በማለት ይማረራሉ፡፡ ህገ ወጥ ናችሁ በሚል ልብሳቸው፣ የቤት እቃቸውና ንብረታቸው ተወስዶ በቀበሌው ግቢ ውስጥ በዝናብ እየበሰበሰ እንደሚገኝ የገለፁት አቶ ጀማል፤ አሁን ሻይ የሚጠጡበት ብርጭቆ እንኳን አጥተው አንዳንድ ሰዎች እያመጡ እንደሚረዷቸው ይናገራሉ፡፡ ”ከ10 ወር በፊት ቤት ተሰርቶ ሊሰጣችሁ ነው እያሉ ሲነግሩን ነበር፤ አሁን ግን የእናንተ በጀት ተቃጥሏል፤ ልንረዳችሁ አንችልም፤ እንደውም አካባቢውን ለቃችሁ ውጡ” እያሉ እያንገላቱን ነው ብለዋል፡፡ “አሁን ገጠር አካባቢ ሁሉ መብራት ገብቷል እየተባለ እንሰማለን፤ እኛ ግን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቤት ስር ቁጭ ብለን ኩራዝ እንጠቀማለን” ያሉት ችግረኞቹ፣ እዚህ መንደር ውስጥ የግልም የመንግስትም ጋዜጠኞች መግባት እንደወንጀል እንደሚቆጠር ይናገራሉ፡፡ “ለመሆኑ እንዴት ልትመጪ ቻልሽ? እዚህ እኮ መግባት የተከለከለ ነው” አሉኝ በግርምት፡፡ ከጭቃውና ከረጃጅሙ ሙጃ ሳር ጋር እየታገልንና ጫማችንን ጭቃ እያወለቀው የላስቲክ መንደሮቹ ጋር ስንደርስ፡፡ ከየትና ለምን እንደመጣን ጠየቁን፡፡ ነገርናቸው፤ ማመን አልቻሉም፡፡

“እኛ በማንም ሳይሆን በፈጣሪ እርዳታ ነው የምንኖረው፤ ለስንቱ ጮህን ግን ጩኸታችንን ወፍ ነው የለቀመው፤ አሁንም ምንም አትፈይዱልንም አንናገርም” አሉ አንድ ጎልማሳ፡፡ ሌላው ደግሞ “በጋዜጣ ብታወጡትም ባታወጡትም ጉዳዩን ጉዳያችሁ አድርጋችሁ ይህን ያህል ብሶታችንን እንድንተነፍስ በማድረጋችሁ እናመሰግናለን” አሉ፡፡ ሌላዋ ወ/ሮ ደግሞ “ሄዳችሁ ለፈለጋችሁት ተናገራችሁ፤ የነገራችኋቸው ቤት ይስጧችሁ” እየተባልን ከዚህም ብሶ ችግር እየፈጠሩብን ተቸግረናል፡፡” እኛ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ነው ያለነው” ሲሉም ተናገሩ፡፡ መረጃውን እንስጥ አንስጥ በሚል በሀሳብ የተከፋፈሉት እኚህ ቅሬታ አቅራቢዎች ከዚህ በፊት መረጃ በመስጠታቸው የደረሰባቸውን ዛቻና ማስፈራራት ይጠቅሳሉ፡፡ እየጮኸች ብሶቷን በለቅሶ የነገረችኝ ህፃን ቃልኪዳን፤ “እኛ ነገ አድገን አገር እንረከባለን፤ እድል ከተሰጠን ብዙ መስራት እንችላለን፡፡ እዛ ደረጃ ለመድረስ ዛሬ ከለላና እንክብካቤ እንሻለን” በማለት አልቅሳለች፡፡

አቶ ጀማል በበኩላቸው፤ “ሚስቶቻችን እሰው ቤት ልብስ አጥበው፣ እንጀራ ጋግረው የገዛነው የቤት እቃችን በቀበሌው ግቢ ውስጥ በዝናብ እየበሰበሰ ነው፣ የልጆቻችን ልብስ ተወስዶ ህፃናት በብርድ ሊያልቁ ነው፤ ልብስና ንብረታችን እንዲመለስልን መንግስትን እንጠይቃለን” ብለዋል። አቶ ቱሉ የተባሉት አዛውንት “እኛ እድሜያችን ገፍቷል፤ የልጆቻችን መጨረሻ ይናፍቀናል፤ አሁን መብራት ስለሌላቸው አይማሩም፤ ወደ ቀን ስራና ልመና ተሰማርተዋል፤ መንግስት መፍትሄ እንዲሰጠን እንማፀናለን” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ “የእናንተ በጀት ተቃጥሏል” አዲሱን ካቢኔ ጠይቁ የሚሉን እኛ አዲስ ካቢኔ ፣በጀት መቃጠል የሚባል ነገር እንዴት እናውቃለን? መንግስት የሚያውቀን የአካባቢው ነዋሪ ነን፤ እንደዜጋ መፍትሄ ይሰጠን፤ እዚህ ወንዝ ውስጥ ተቀምጠን ጅብ ቢበላን ለመንግስት ለራሱ ስምም ጥሩ አይደለም” በማለት ተማፅነዋል፡፡ ስሟን መጥቀስ ያልፈለገች አንዲት ሴትም፤ “ለ18 እና 20 ዓመት በቀበሌ ጉዳዮች ስንሳተፍ በእድር ተካተን ወልደንና ከብደን በኖርንበት አካባቢ መንግስት አላውቃችሁም ማለቱ አሳፋሪ ነው፤ በመንግስት ተስፋ ቆርጠናል፤ አሁን ፈጣሪን የሚፈሩ ባለሀብቶች እንዲታደጉን እንጠይቃለን” ብላለች፡፡ ጉዳዩ የሚገኝበት ወረዳ ሄደን ለማጣራት ሙከራ ያደረግን ሲሆን ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሀላፊ በዚህ ሳምንት አይገኙም የሚል ምላሽ በማግኘታችን የወረዳውን ምላሽ ማካተት አልቻልንም፡፡

Published in ዜና
Page 17 of 17