Saturday, 17 August 2013 12:07

ጋሽ ስብሐትን በጐሪጥ

“መልክዐ-ስብሐት” በሚለው የአለማየሁ ገላጋይ መፅሐፍ ውስጥ በተካተተው የሚካኤል ሽፈራው መጣጥፍ ላይ ያቀረብሁትን አስተያየት ተከትሎ “ጤርጢዮስ ከቫቲካን” የለመደውን አስተያየቱን ይዞ መጣ፡፡ መምጣቱስ ባልከፋ፡፡ አስተያየቱ ክፉኛ ተጠናገረብኝ እንጂ፡፡ ለወትሮም ሳር ቤት አካባቢ ካለችው ቫቲካን መንደር ውስጥ ምዕመናን ሳያውቁት ቆብ የደፋ ጳጳስ ይመስለኝ የነበረው ወዳጄ ጤርጢዮስ አሁንማ ብሶበት አገኘሁት፡፡ ሚካኤልን ለመከላከል እየተደነባበረ በእንቅልፍ ልቡ የፃፈው የሚመስለው መጣጥፉም ፍሬ የለሽ ሆነብኝ፡፡ ለስብሐት ካለኝ “ራሮት” የተነሳ የአለማየሁን ግብዣ ሳልቀበል ቀረሁ የሚለን ርህሩህ መሳዩ ጤርጢዮስ፤ የጀመራትን አረፍተ ነገር በአራት ነጥብ ሳይዘጋው ነው በሚካኤል ጭካኔ “እጅግ” ደስ እንደተሰኘ እና ልቡ ቅቤ እንደጠጣ የሚነግረን፡፡ ከዚህም ሌላ ሚካኤል ባነሳውና የስብሐት ኢኮኖሚያዊ ድህነቱ ምክንያት ነው ባለው ስንፍና፣ እንዲሁም ስራ ፈትነት እና ጊዜን በዋዛ ፈዛዛ ማሳለፍ በተጨማሪ እኔ የመለስኩትን ምላሽ እንደ ለመደው ጣቢያ በመቀላቀል በግብረገባዊ እና ሃይማኖታዊ አውድ ከስሶኛል፡፡ ከዚህ የበለጠ መጠናገርም፣ መደናገርም፣ መቀላመድም ከየት ይመጣል? ምናልባት ዳግመኛ ከቫቲካን ካልመጣ በቀር! ስለዚህ ለጤርጤዮስም መልሴ ዝምታ ነው፡፡ ይህቺን ታህል ካልኩት ይበቃዋል፡፡ እሷኑ ይባርክለት፡፡
የዛሬው ፅሁፌ ምክንያት ባለፈው በዚሁ ጋዜጣ ላይ በወጣው ፅሁፌ ውስጥ ግርታን ሊፈጥር የሚችል ነገር የተናገርሁ ስለመሰለኝ፣ በዛ ዙሪያ ጥቂት ለማለት ነው፡፡ ፅሁፌ ውስጥ ስብሐትን የጐሪጥ የማይ ሰው መሆኔን የምትጠቁም አረፍተ ነገር ነበረች፡፡ አረፍተ ነገሯ ግራ ሳታጋባ እንደማትቀር ጠርጥሬያለሁ፡፡ እነ ጤርጢዮስ የስብሐት አወዳሽ ያደረጉኝ ለዚህ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ማን ያውቃል - ወዳጆቹ ደግሞ ጠላቱ የሆንኩ ይመስላቸው ይሆናል፡፡ እኔ ግን ወዳጁም ጠላቱም አይደለሁም፡፡ ታዛቢው/ተመልካቹ ነኝ ብል ይቀለኛል፡፡ የምታዘብበት ጥግ አለኝ፡፡ ጥጌ እምነት ነው፡፡ እምነቴ ክርስትና ነው፡፡ ክርስትናዬም ድሮ “ጴንጤ” ይባል ነበር፡፡ ዛሬ ሌላ ስም ሳያስፈልገው አይቀርም፡፡
እምነቴ ከመፅሐፍ ቅዱስ ቃል ጋር እስከተስማማ ድረስ ሌላ እምነት ያለውን ሰው አመለካከት እና ፍልስፍና እውነትነት መቀበል ብሎም መጠቀም እንደምችል ያደፋፍረኛል፡፡ ምሳሌ ልጥቀስ፡፡ ቀደምት የወንጌል አድራሽ ሐዋርያ የነበረው ጳውሎስ፤ በጥንቷ የአቴና ከተማ አዲሱን ወንጌል በማዳረስ ተልእኮው ሳለ፣ ፈላስፎች እና የፍልስፍና አፍቃሪዎች ይሰበሰቡበት በነበረ አርዮስ ፍጐስ በተባለ አንድ አዳራሽ መካከል ቆሞ ወንጌል ሰብኮ ነበር፡፡ በስብከቱ ውስጥ ታዲያ ኤፒዴንዴስ፣ አራጠስ እና ቅሊንጦስ የተባሉ ታዋቂ የግሪክ ባለቅኔዎችን ስራ ጠቅሷል፡፡
ስለዚህ እኔም የመፅሐፍ ቅዱስን ሃሳብ የሚያስተጋቡልኝን አንዳንድ የስብሐት አስተሳሰቦች እና አመለካከቶች እውነትነት ብመሰክር፣ በእነርሱም ብጠቀም ኃጢአት አይሆንም፡፡ ከመፅሐፍ ቅዱሳዊ አስተሳሰቦች ጋር የሚስማሙ ሃሳቦችን ከስብሐት ሥራዎች ውስጥ ነቅሶ ማውጣት ግብዝነት የሌለበት ትህትናን፣ ጥንቃቄን እና ብስለትን ይጠይቅ እንደሆን እንጂ ሞልቷል፡፡ እዚህ ላይ “እውን ከስብሐት በጐ ነገር ይወጣል?” ብሎ የሚጠይቅ የዋህ አንባቢ እንደማይጠፋ አስባለሁ፡፡ ስብሐት ሪያሊስት እና ሱሪያሊስት ፀሐፊ እንደነበር የታወቀ ነው፡፡ በሪያሊዝም ዘውግ ውስጥ በሰራቸው ስራዎች የግለሰቡን እና የማህበረሰቡን ድብቅ ገበያ እየበረበረ (በርሱ አባባል ጉድ ጐልጓይ ጓድ እየሆነ) ሰው ምን ቢማር ደንቆሮ፣ ምን ቢሰለጥን አውሬ፣ ምን ቢያምር ጭቃ፣ ምን ጨዋ ቢሆን ወራዳ እንደሆነ፣ የህይወትን አያዎ (Paradox) እና የማይጣሰውን እና በሁሉም ፍጥረት ውስጥ የሚሰራውን ሚስጥራዊ የሰናይ እና እኩይ አፍራሽ እና ገንቢ ኃይላት መኖር (Presence) አሳውቋል፡፡ እነዚህ እውነታዎች (Realities) ደግሞ በተቻለ መጠን ከራሱ ለመሸሽ እንጂ ራሱን ለመጋፈጥ እና ለማሸነፍ ለማይፈልገው የሰው ልጅ እና ለዚህ አላማው እንዲረዳው ለፈጠረው “ማህበረሰብ” አስጊ እና አደገኛ በመሆናቸው ፈፅሞ የማይቀበላቸው እና እሴቶቼ ብሎ ከያዛቸው ጋር የሚጋጩ ናቸው፡፡ ስብሐት በህይወቱ እና በስነ-ፅሁፍ ስራዎቹ የተጋፈጣቸው የእነዚህ እውነታዎች መራርነት እና አስጨናቂነት አያጠራጥርም፡፡ ለዚህም ነው የእርሱን ሪያሊዝም ከአፉ እየተቀበሉ የተጋቱት እንደ አቶ ሚካኤል ያሉ ራስን ስለማጥፋት ያስቡ የነበረው (ፍልስምና 2 ይመልከቱ) ወይም ደሞ እንደ ጤርጤዮስ ያሉ “ለማበድ አንድ ሀሙስ” እስኪቀራቸው ድረስ አእምሮአቸው የታወከው፡፡ ለዚህም ነው ስብሐት እራሱ ከዚህ አስጨናቂ እና አሰልቺ እውን አለም ሾልኮ የሚወጣበት ሌላ የሥነ-ፅሁፍ ዘውግ (Surrealism) የሞከረው፤ ለዚህም ነው በሀሺሽ እና በአረቄ እየፈዘዘ እና እየደነገዘ እውኑን አለም ለማለፍ (Transcendence) የሞከረው፡፡ ነገር ግን ይህን እና ይህንን የመሳሰሉት የስብሐት እና የተከታዮቹ አሉታዊ ልምምዶች ሞት አሊያም አደንዛዥ እፅ፣ አሊያም እግዚብሔርን የሚያስመርጠውን የዚህን አለም መራራ፣ አሰልቺ እና ትርጉም የለሽ ህልውና አድምቀው እና አጉልተው ያሳዩ እንደሆነ እንጂ ውሸት አሊያም ቅጥፈት አያደርጉትም፡፡ ፀጋ ተሞልታ በሰው በልቡና ካላደረች በቀር ራቁቷን የታየች እውነት አደገኛ ለመሆኗ ምስክር ናቸው፡፡
የስብሐት “ሰው” እና መፅሐፍ ቅዱሴ ከእግዚብሔር ውጪ ስላለ “ሰው” የሚነግረኝ ተመሳሳይነት አላቸው፡፡ ሁለቱም ስለሰው ልጅ መጥፋት፣ ስለሰው ልጅ ለከንቱነት መዳረግ፣ ስለሰው ልጅ አይለወጤነት እና በስብሐት አባባል “ቢልጡት ሽንኩርትነት”፣ ስለሰው ልጅ እንስሳዊነት፣ ሰይጣናዊነት፣ ጠፊነት፣ እብደት… ይነግሩኛል፡፡ መፅሐፈ መክብብም መፅሐፈ ስብሐትም “እነሆ ከንቱ፣ ከንቱ፣ የከንቱ፣ ከንቱ ሁሉ ከንቱ ነው… ከፀሐይ በታች በሚደክምበት ድካም ሁሉ የሰው ትርፍ ምንድን ነው?” ብለው የህይወትን ትርጉም ፈልገው ያጣሉ፡፡ ተስፋ ይቆርጣሉ፡፡ ነገር ግን ባንድ ነገር ይለያያሉ፡፡ ከሰማይ በላይ ባለው ነገር! ስብሐት ሐሺሹን፣ ወሲብን፣ እና ሱሪያሊዝም ዘውግን ከእውነት አለም የሚድንባቸው ሶስቱ ሥላሴ አድርጐ አምኗቸው ኖሮ አምኗቸው ሞቷል፡፡ መፅሐፍ ቅዱሴ ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ስላለው መዳን ያወራል፡፡ ስብሐትን በስስት አይን ሳላየው፣ አሊያም ደግሞ እንደነጠርጤዎስ ሳላጉረጠርጥበት እንዲያው የጐሪጥ ብቻ ላየው የቻልኩበት ሚስጥሬ እንግዲህ ይኸው ነው፡፡ ቅንነቱ እና እውነት በተገኘችበት ቦታ ሁሉ ለማበር ፍላጐቱ ያለው ማንም ሰውም አብሮኝ ሊሆን የማይችልበት ምክንያት አይታየኝም፡፡
ስለራሴ ይህን ካልኩ አሁን ደግሞ ስብሐት ላይ ስለሚያጐረጠርጡበት በተለይም ከሃይማኖት ጐራ ውስጥ ሆነው ስለሚፎክሩበት ሰዎች ጥቂት ልበል፡፡ እነዚህ ፎካሪዎች የተቋም ሎሌዎች ናቸው፡፡ ያሉበትን የሃይማኖት ተቋም ህልውና ስጋት ላይ የሚጥል ማንም ሰው ቢመጣ ዱላ (ብዕር፣ አፍ፣ ቡጢ፣ መሣሪያ…) ከመምዘዝ ወደ ኋላ አይሉም፡፡ እግዜር ራሱ እንኳ ቢሆን አይለቁትም፡፡ The Brothers Karamazov የተሰኘው የዶስቶይቭስኪ ልቦለድ ውስጥ The grand inquisitor የተሰኘው የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስትያን ደህንነት ጠባቂ ገፀ ባህርይ፣ ኢየሱስ በሰው አምሳል ዳግመኛ ወደ ምድር ተመልሶ ለሰዎች በጐ ነገር ሲያደርግ ባገኘው ጊዜ አሳስሮት በጥያቄ እያጣደፈ ሲወነጅለው እና ሲከሰው ይታያል፡፡ ይህ ችግር የክርስትና ሃይማኖት ተቋማት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ሃይማኖት ተቋማት ችግር ነው፡፡ ምናልባትም የሃይማኖት ተቋማት ብቻ ሳይሆን የተቋማት ሁሉ ችግር ነው ቢባል ሳይቀል አይቀርም፡፡ ተቋምን የአገልግሎት መሳሪያ (means) ከማድረግ ይልቅ ተቋምን ቅዱስ እና አምላክ የሆነ ይመስል ማገልገል አብዝቶ የተለመደ ነው፡፡ እራስን ከተቋም ጋር ማስተሳሰር፣ ከተቋም እግር ስር መስገድ፣ ለተቋም ክብር እና ህልውና ህይወትን እስከመሰዋት ድረስ ዋጋ መክፈል እና ማስከፈል በተለይ በፖለቲካና በኃይማኖት ተቋማት አካባቢ አዲስ አይደለም፡፡ በተቋማዊ ፍቅር እና አክብሮት ሰበብ ግለሰባዊ መብትንም ሆነ ግዴታን መሰዋትና ማምለጥ ተራ ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ የሃይማኖት እና የማህበረሰቡ ጠባቂዎች ነን ብለው ከሚያስቡ ሰዎች ስብሐት የከፋ ስደት እና ተቃውሞ ቢደርስበት የሚገርም አይሆንም፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በባህርያቸው ያለማቋረጥ ስለ ኃጢአት እና ስለ ፅድቅ በሚሰበክባቸው የሃይማኖት ተቋማት አካባቢዎች እንደ ስብሐት አይነቱ ሰው ስም ያለቦታው ሲነሳ እንዴት ባለ ፍርደ ገምድል (Prejudicial) ሚዛን ላይ ተቀምጦ እንደሚብጠለጠል መገመቱ አያስቸግርም፡፡
ለአንበሳ እንደተወረወረለት ስጋ ይቀራመቱታል፡፡ ሀቁ ግን በፅድቅ ስም እንዲህ ያለ የግብዝነት ሥራ የሚሰራው ራስን ለማፅደቅ እና የራስን ፅድቅ ለማጉላት ካለ ውስጣዊ ፍላጐት ተነሳሽነት መሆኑ ነው፡፡
እንዲያማ ባይሆን ለሃይማኖታቸው የቀኑ የሚመስሉት እንደ ጠርጢዎስ አይነቶቹ ሰዎች ስብሐትን አገሩን በሞላ ያሳተ ቀንድ እና ጅራት ያለው ሴጣን አድርገው በመሳል ፈንታ፣ መሰረታዊ የክርስትና እምነት እንደሚያስተምረው፣ እርሱም እንደማንኛውም ሰው አዳማዊ የውርስ ኃጢያት (original sin) ያለበትና እርሱም በእኩይ ተፅእኖው አሳታቸው ተብለው ከንፈር እንዲመጠጥላቸው እንደሚፈልጉት ተከታዮቹ ሁሉ እርሱም ራሱ ከንፈር ሊመጠጥለት የሚገባ እንደሆነ በቅድሚያ ማመን ነበረባቸው፡፡ ምክንያቱም ስብሐት ራሱ ለትምህርት ሲል በሄደበት ቦታ ለምዕራቡ አለም ፍልስፍና ተፅእኖ የመጋለጥ እጣ ፈንታ የወደቀበት አንድ ምስኪን ኢትዮጵያዊ ወጣት ነበርና!
ጥቂት ስለ ስብሐት ደጋፊዎች
ስብሐት ብዙ ደቀመዛሙርት ያፈራ ሰው ሊመስል ይችላል፡፡ እኔ ግን አይመስለኝም፡፡ ወደ እድሜው ማክተምያ አካባቢ የቅርቡ ነን ይሉ ከነበሩ ሰዎች ጋር እንኳ ሰላም እንዳልነበረው የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ሲጀመር ስብሐት እውነተኛ ደቀመዝሙር እንደነበረውም እጠራጠራለሁ፡፡ በግርግር የተከተሉት እና በሩቅ የሚያደንቁት አያሌ እንደነበሩ ግን ግልፅ ነው፡፡ ስብሐት አድናቂ፣ ካቢ፣ አወዳሽ፣ በትከሻው ላይ ተንጠላጥሎ የሚወጣ እና የሚወርድ እንጂ እውነተኛ የፍልስፍናው ወራሽ እና ተከታይ የነበረው አይመስለኝም፡፡ ቢኖረው እንኳ ከጣት ቆጠራ አያልፉም፡፡ እውነቱ እንዲህ ከሆነ የስብሐት ደጋፊዎች ለምን እንዲህ እንደ አሸን ፈሉ? የደጋፊዎቹስ ስነ-ልቡና ምን አይነት ነው? ምናልባት ይሄ ራሱን የቻለ ጥናት ያስፈልገው ይሆናል፡፡ እኔ ግን የመሰለኝን ልጠቁም እና ልሰናበት፡፡ የግሪክ ትራጄዲዎችን የሚያጠና የሥነ-ፅሁፍ ክፍል አለ፡፡ ዘርፉ ከሚጠይቃቸው ጥያቄዎች መካከል በታሪኩ ውስጥ በገፀባህርያቱ የሚጣሰው ከባድ ማህበረሰባዊ/ሃይማኖታዊ ህግጋት እና በተመልካቾቹ አቀባበል መካከል ያለው አያዎ (Paradox) ነው፡፡ በአንዳች ክፉ እጣ ፈንታ ተይዘው አባታቸውን ለገደሉ፣ እናታቸውን ላገቡ፣ በአማልዕክቶቻቸው ላይ ላመፁ ገፀባህርያት ተመልካቹ በጋለ ስሜት ለምን እንደሚያጨበጭብላቸው ይጠይቃል፡፡ ለዚህም ከሚሰጡት ምላሾች መካከል አንዱ የሚከተለው ነው፡፡ የሰዎች ልብ ውስጥ የማህበረሰቡን ህግጋት የመጣስ ተፈጥሯዊ ዝንባሌ አለ፡፡ ነገር ግን አብዛኛው ሰው ማህበረሰቡን በመፍራት ይህን ዝንባሌውን እና ፍላጐቱን አምቆ በመያዝ ህግጋቱን እያከበረ ይኖራል፡፡ በዚህ መሃል የማህበረሰቡን ህግጋት የሚፈታተኑ እና የሚጥሱ ብርቱ እና ጠንካራ ሰዎች ሲመጡ አርአያታቸውን ለመከተል ድፍረት ባይኖረውም እነርሱን ለመደገፍ እና ለማድነቅ ያህል ግን ድፍረት አያጣም፡፡

Published in ጥበብ

የአገራችን ኪነጥበብ በተለይም ሙዚቃውንና ስነፅሁፉን የተጣባው አንድ መጥፎ አመል አለ፤ እሱም የገዘፉ ስሞች ላይ በመንጠልጠል ትራፊ ዝና የመልቀም አባዜ ነው፡፡ እንዲህ አይነት የብልጣብልጥ አካሄድ ብዙ አሉታዊ ውጤት ሲፈጥር ይታያል፡፡ ሁለቱን ልጥቀስ፡፡ ቀዳሚው መንጠልጠልን ተከትሎ የሚመጣ የዝና ቁራጭ ወደ ራስ እንዳይመለከቱ ስለሚያዘናጋ ነው፡፡ ስንቶቹ በሌሎቹ ላይ ተመስጠው ራሳቸውን ሳይሆኑ ባክነው ቀርተዋል? ማንነቱን ራሱ ላይ ያልገነባ ሰው የትም አይሄድም፤ ከተንጠለጠለበት ግንድ ላይ እየተወዛወዘ ከብት መንጃ የእረኛ ለበቅ እስኪሆን ይጠብቃል፡፡ ሁለተኛው የመንጠልጠል ክፉ ውጤት ወረርሽኝነቱ ነው፡፡ የሃሳብ ጥገኝነት ከአንዱ ወደ አንዱ እየተላለፈ ትውልዱን ሲቆጣጠር የትኩረት ማዕከል አንድ ስፍራ ላይ ይሆንና በተለይ በኪነቱ ዘርፍ ሲሆን ፈጠራ ይሞታል፡፡ ከአንድ ፋብሪካ የወጡ የሚመስሉ ዘፈኖችን የምንሰማው እና አንድ አይነት ጭብጥ እና ቅርፅ የያዙ ድርሰቶችን የምናነበው ወይም ፊልሞችን የምናየው ለዚህ ነው፡፡
እርግጥ ነው ከተንጠለጠሉበት ‹ግንድ› በተገቢው ሰዓት መውረድ ከተቻለ መንጠልጠል በራሱ ችግር ላይኖረው ይችላል፡፡ ለዚህ ድምፃዊ ቴዲ አፍሮ ጥሩ ምሳሌ ይመስለኛል፡፡ ቴዲ ንጉስ ሃይለ ስላሴ ላይ፤ ሃይሌ ገብረስላሴ ላይ፤ ጥላሁን ገሰሰ ላይ…….ወዘተ …….ተንጠልጥሎ ቆየና ሰዓቱን አየት አድርጎ ዱብ አለ፡፡ ራሱን ቻለ፡፡ ከመንጠልጠል ወደ ማንጠልጠል ተሸጋገረ፡፡ መንጠልጠል መንጠልጠልን ስለሚወልድ ችግር ቢሆንም በተገቢው ሰዓት ራስን ችሎ መቆም መቻልም አንድ ነገር ነው፡፡ ክፋቱ ብዙ የኪነጥበብ ሰዎች ላይ ተንጠልጥሎ የመቅረትን ኪነት ብቻ ነው የምናየው፡፡
በኢትዮጵያ የስነፅሁፍ ታሪክ ሳይፈልግ ሰዎች እየተንጠለጠሉበት የተቸገረ ሰው ቢኖር፣ ደራሲ ስብሃት ገብረ እግዚአብሔር ይመስለኛል፡፡ ስብሃት ላይ እየተንጠለጠሉ ካስቸገሩ እና በተለይ ደግሞ በቅርቡ በታተመ ‹መልክአ ስብሐት› መፅሃፍ ላይ ይህ አመል ከበረታባቸው ፀሃፍት መካከል አንድ ሁለቱን ለነገር ከመጥራቴ በፊት ስብሐት ለኔ ምንድን መሆኑን ልናገር፡፡
በእኔ እምነት ስብሐት ገብረ እግዚአብሄር የኢትዮጵያ ዘመናዊ ስነፅሁፍ አውራ (mastermind) ነው፡፡ ሐዲስ ዓለማየሁ በበቅሎ ጭነው አባይን ያሻገሩትን የዘመናዊ ስነፅሁፍ ጓዝ፣ በመንኮራኩር ወደ ህዋ ያመጠቀው ስብሐት ገብረእግዚአብሔር የተባለ የለውጥ ሃይል ነው፡፡ እስኪ ላፍታ….ስብሃት አፍላ ጎረምሳ እንዲሁም ጎልማሳ በነበረበት ዘመን የነበረውን ትውልድ አስቡት፡፡ ገሚሱ በጭፍን ያገር ፍቅር ስሜት የነደደ ሲሆን ቀሪው ደግሞ ከፈረንጅ በወረሰው ጥራዝ ነጠቅ ርዕዮተ-ዓለም የሚንጠራወዝ ሙትቻ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ አይነት ጠርዝ የያዙ አደገኛ ስሜቶችና አስተሳሰቦች ትናጥ የነበረች ምስኪን አገር ነበረች፡፡ የትውልዱ መጨረሻ ያላማረውም ለዚህ ነበር፡፡ ስብሐት ከብዙ ንፍሮ መሐል የተገኘ አልማዝ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህ ነው ፈጣሪ በሰጠው ሙያው ከዘመንኞቹ በተሻለ ለዚህ ትውልድ የበቃ ቁም ነገር ሊያተርፍ የቻለው፡፡ “ስምንተኛው ጋጋታ”ን የመሰለ ፋንታሲ ልቦለድ በዚያ የድርቅና ዘመን ሊፈጥር የሚችል ምን አይነት ታላቅ ልቦና ነው? ስብሐት በስራዎቹም ሆነ ድርሰት በሚመስለው ህይወቱ ተፅዕኖ ያላሳደረበት ፀሃፊ ነኝ ባይ ያለ አይመስለኝም፡፡ እነ አዳም ረታ ህፅናዊነት፤ እንጀራ…ወዘተ….እያሉ ስም የሚያወጡለት ለአገራችን ስነፅሁፍ እንግዳ የሆነ አፃፃፍ ምንጩ ስብሐት ነው፡፡ (የአንስታይን አንፃራዊነት ስሌት ህይወት ማግኘት የቻለው በነ ማክስ ፕላንክ የሂሳባዊ ቀመር ፈጠራዎች ነው፡፡ ስብሐት ማክስ ፕላንክን ይመስለኛል፤ የፈጠራ ሊቅ፡፡) አንድ ሐሳብ ለመናገር አንድ አንቀፅ ወይም ገፅ የሚጨርሱ ደራሲያን ዕልፍ በነበሩበት ዘመን፣ በአምስት ቃላት ብቻ ምን የመሰለ ሃሳብ መናገር እንደሚቻል ያሳየ ሰው ቢኖር ሊቁ ስብሐት ነው፡፡ የዚህ ዘመን ራስ ወዳድ ፀሐፍት ደፋሩ ስብሃት ቀድሞ በገሰሰው የባህል ድንግልና እንደልባቸው መውጣትና መግባታቸውን ማመን ቢተናነቃቸውም ቅሉ እውነቱ ግን ስብሐት የስነፅሁፍ ሙያ ነፃነት እስከምን መጓዝ እንዳለበት ያሳየ ባለውለታቸው መሆኑን ውስጣቸው ይነግራቸዋል፡፡ ስብሃትን ትልቅ የሚያሰኘው አካፋን አካፋ ብሎ መጥራቱ ወይም መፃፉ አይደለም፤ የስብሐት ቁምነገረኛነት የሚንፀባረቀው ለሁላችንም በፈጠረው የድርሰት ነፃነት ሜዳ ነው፡፡ ምናልባትም ስብሃት ባይደፍረው ዛሬም ድረስ ወሲብን ከርክሞ መፃፍም ያስነውር ነበር፡፡ ስብሐት የአገራችን ስነፅሁፍ ይዘት፤ ቅርፅ እና እይታ ከተለመደው ይወጣ ዘንድ ከባድ መስዋዕትነት ከፍሏል፡፡ “መልክዓ ስብሐት” በሚለው መፅሃፍ ሚካኤል ሽፈራው የተባለ ፀሃፊ ስብሐትን ስነምግባር የጎደለው፤ አረቂያም፤ ጫታም፤ ድሃ፤ ሰነፍ……..ወዘተ….. ለማለት አርባ ገፅ ሙሉ መቁጠሩ የስብሐት መስዋዕትነት አንድ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡ ለነገሩ ለእኔ ከመፅሃፉ አርታዒ አለማየሁ ገላጋይ ጋ ሸንጎ ተደርጎበት የተፃፈው የአቶ ሚካኤል ሽፈራው ፅሁፍ ከመንጋው ተነጥሎ ለመታየት የተሞከረ የመታየት አምሮት ያንጠራወዘው ሞኝነት ነው የሚመስለኝ፡፡ (ምክንያቶች አሉኝ፤ እመለስባቸዋለሁ፡፡)
የዘመኑ ፀሃፍት መሰረታዊ ችግር አጉል ብልጠት ነው፡፡ አስቂኝ የሆነው ነገር ደግሞ ብልጠታቸው ብልህነት ስለማይታከልበት ፈጥነው በትዝብት ገመድ ተጠልፈው ይወድቃሉ፡፡ ብልጠቱን መደበቅ ያልቻለ ሰው ከሞኝ በምን ይለያል?
እንግዲህ ይህን ፅሁፍ ለመፃፍ የተነሳሁበት መሰረታዊ ምክንያት እኔም ሲያደርጉ እንዳየሁት፣ ስለ ስብሐት የመናገር ዛር ለክፎኝ ሳይሆን በ”መልክዓ ስብሐት” መፅሃፍ በሁለት ተቃራኒ አቅጣጫ ስብሃት የታየበት መንገድ ስላሳሰበኝ ብቻ ነው፡፡ በእኔ እምነት “መልክዓ ስብሐት” ገፅ 67 ላይ ተጠናቋል፡፡ የስብሐትን ስራዎች እንዴት ማየት እንዳለብን ቴዎድሮስ ገብሬ ከበቂ በላይ ትንታኔ ስላደረጉ ላመሰግናቸው እፈልጋለሁ፡፡ በመጨረሻው ገፅ የቀረበውን የፀደይ ወንደሙን ምሁራዊ ትንተና ሳይጨምር ከገፅ 67 በኋላ ያለው መልክዓ ስብሐታዊ ዝርዝር ትርፉ ትዝብት ብቻ ነው፡፡ ሁሉንም ትዝብቶች በጋዜጣ ሜዳ ተናግሮ መጨረስ ስለማይቻል የባሱት ላይ ማተኮር ይሻላል፡፡ እናም ስብሐትን ወደ ቅድስና እና እርኩሰት ከወሰዱት የአለማየሁ እና የሚካኤል ፅንፍ ዕይታዎች ላይ በማተኮር የሚከተለውን ልበል፡፡

የሚካኤል ሽፈራው ስብሐት
በዚህ የአገራችን ‹አፍሮጋዳ› ዘመን እንደምናጤነው ነገርን ማጦዝ ቢያንስ ሁለት አይነት ትርፍ ያስገኛል፤ የስም እና የገንዘብ፡፡ በዚህ መሰረት ጓደኛሞቹ አለማየሁና ሚካኤል ስብሃትን በማጎን እና በመፈጥፈጥ ያገኙትን ትርፍ ‹ኦዲት› አድርገው ያወራርዱ ዘንድ በስብሐት የነፃነት ነፍስ ስም ብንጠይቅ ነውር የለበትም፡፡ ለነገሩ ተመካክሮ መፃፍ በራሱ ችግር የለውም፡፡ ችግሩ ሊፃፍለት የሚገባውን ጉዳይ ወይም አካል በትክክል ሳይገልፁት ሲቀሩ ይባስ ብሎም አበላሽተውት ሲገኙ ነው፡፡ በዚህ መሰረት ቢያንስ በኔ እይታ በ”መልክዓ ስብሐት” አለማየሁ እና ሚካኤል ስብሐትን የፃፉበት ወረቀት ያሳዝነኛል (እንዲህ በተወደደ ወረቀት!)፡፡ እኛ እንደምናውቀው ስብሐት ሰው ሆኖ ኖሮ እንደ ሰው ያለፈ ሰው ነው፤ ከዚህ የወጣ ከዚህ የወረደ ነገር የለም!
አርባ ገፅ ሙሉ ስለ ስብሃት ድህነት እና ምግባረ ብልሹነት መፃፍ፣ ፀሃፊውን ከማስገመት የዘለለ ትርጉም የለውም፤ መፃፍ መቻል እውነትን መፃፍ ሊሆን አይችልምና፡፡ እንደ ዱባይ ህንፃዎች አለቅጥ የረዘሙ የሚካኤል ሽፈራውን አረፍተ ነገሮች በማየት ብቻ ሲጀመር ሚካኤል የስብሐት ተከታይ እንዲሆን የሚያስችል አፈጣጠር እንደሌለው መጠርጠር ይቻላል፡፡ ተከታይ መሆንስ ምንድን ነው? አሪፍነት ነው እንዴ? እነ ሚካኤል በወጣትነታቸው እነ ስብሐት ስር ተኮልኩለው ተባራሪ ሃሳብ ከመቃረም እንደ ስብሐት መፅሐፍ ቢገልጡ ነበር የሚያዋጣቸው፡፡ ጥገኝነትን መሻት በራሱ ስንፍና እንዲሁም በራስ ያለመተማመንን ማሳያ ነው፡፡ የሆነ ሆኖ አንድ ሰው የሌላ ሰው ተከታይ የሚሆነው ከሰውዬው አዕምሮ የሚወጡ ሃሳቦችን ለማጥመድ ብቻ መሆን አለበት፡፡ …..እንጂ ስብሐት ቢፈልግ እንኳን በመለኪያ ቀርቶ በጋን አረቄ ቢያንዶቀዱቅ የተከታዩ ችግር መሆን አልነበረበትም፡፡ እንደገባኝ ሚካኤል ከስብሐት መማር የፈለገው የግብረገብ ትምህርትን ነበር፡፡ እንዲህ ከሆነ ወደ ስብሐት ሲሄድ በጣም ተሳስቶ ነበር ማለት ነው፤ ምክንያቱም ስብሐት የቄስ ልጅ እንጅ ቄስ አይደለም፡፡ ስብሐት ደራሲ እንጂ የስነስርዓት መምህር አልነበረምና ያልተሰጠውን መክሊት መጠበቅ አንድም ስብሐትን አግንኖ ከማየት ይመነጫል አሊያም ራስን አሳንሶ ከመመልከት፡፡
እንደ አለማየሁ ገላጋይ እና ሚካኤል ሽፈራው ስብሐት እግር ስር ቱስ ቱስ የማለት አጋጣሚ ባይኖረኝም የስብሐት አድናቂ ነኝ፡፡ አድናቆቴ አክብሮትም አለው፡፡ ከአረቄ ጠጭነቱ ሌላ ብዙ መጥፎ ነገሮች የሚወሩበት ስብሐት ግን በእኔ ህይወት ላይ የፈጠረው አሉታዊ ነገር የለም፤ ብችል እንደ ስብሐት ለመፃፍ እፍጨረጨር ይሆናል እንጂ እንደ ስብሐት አረቄ ለመጠጣት አልጣደፍም፡፡ ከስብሐት እውቀቱን እንጂ ጫት አበጣጠሱን ከተማርኩ ደካማው እኔው ራሴው ነኝ፡፡ ስብሐት ሰው ነው እና እንደማንኛውም ደካማ ጎኖች ነበሩት፡፡ ሚካኤል ከስብሐት ጥንካሬውን ሳይሆን ድክመቱን ከተማረ ደካማው ራሱ ነው፡፡ እንዲያውም በታላላቆቹ መጥፎ ባህሪ ስር የሚጠለፍ ትውልድ ይቺ አገር አያስፈልጋትም፡፡ ራሱን መቆጣጠር የማይችል ትውልድ አገሩንም መቆጣጠር ወይም መጥቀም አይችልም እና ኖረም ሞተም ያው ነው፡፡ እንዲያውም ሸክም ከሚሆን ደካማው ጠፍቶ ጠንካራው አገር ቢረከብ ይሻላል፡፡ በስብሐት መጥፎ መንገድ ተመርተው የጠፉ ወጣቶች ካሉ እኔ እንኳን ጠፉ ተመስገን ነው የምለው፡፡ ምክንያቱም እያንዳንዱ ዜጋ ወይም ትወልድ ራሱን የማበጀት ዕዳ እንዳለበት ነው የማምነው፤ ካልቻለ ግን ምን ይደረጋል መቃብሩን አስፍቶ መቆፈር ነው፡፡ ስለዚህ በራስ ጣጣ አንድ ስብሐትን መውቀስ ራስን ከማስናቅ አያልፍም፡፡ ሚካኤል ጭቆና ስለለመደ የስብሐት ነፃነት አፍቃሪነት ካልተስማማው ከጨቋኞች ጋር መቧደን ነው ያለበት፡፡
ሚካኤል ከስብሐት ስራዎቹ እና ስነፅሁፋዊ ተፅዕኖው ይልቅ ግብረገቡ ላይ ማተኮሩ መቼም ሁሌ ባሰቡት ቁጥር የሚያስቅ ነገር ነው፡፡ ጋዜጠኛ እቱ ገረመው እዛው “መልክዓ ስብሐት” ላይ ባሰፈረችው ሃሳብ ሁሉንም ተናገረችብኝና መድገም ሆነብኝ እንጂ እንደ እውነቱ ከሆነስ ስብሐት በትህትናውም ቢሆን የሚታማ ሰው ሆኖ አልነበረም፡፡ እስኪ አስቡት ‹‹ስለ እኔ አያገባችሁም፤ የራሳችሁን ኑሮ ብቻ ኑሩ!› ከማለት የበለጠ ትህትና የት ይገኛል? ከስብሐት በስተቀር እንዲህ የሚል ኢትዮጵያዊስ ማነው? ይሄ ትውልድ የተቸገረው እናውቅልሃለን የሚሉት ስለበዙ ነው፡፡ ብናስተውል ለሰው ልጅ ነፃነትን የመሰለ ታላቅ ስጦታ የለም፡፡ የሚካኤል ሽፈራው ጓደኞች የነፃነት አያያዝ አላማረምና ስብሐት በምን ዕዳው ይወቀሳል፡፡

የሚካኤል ሽፈራው ያልተገናኝቶ ንፅፅሮች ስብሃትና ፀጋዬ
ሚካኤል ሽፈራው ስብሐትን ለማጋለጥ በፀጋዬ በኩል መጣና የጋሽ ፀጋዬን ገመና አጋልጦ አረፈ፡፡ በበኩሌ የጋሽ ፀጋዬ በጅምላ የመረሸን አመል እና አግናኝነት ደስ አይለኝም፡፡ ‹‹ጫታም ትውልድ….›› ብሎ መዘርጠጥ ቢያንስ ከሎሬት ፀጋዬ አይጠበቅም፡፡ የመቅደላው ቴዎድሮስና የፀጋዬ ቴዎድሮስ አራምባና ቆቦ ናቸው፡፡ እውነቱን ዘጭ አድርጎ የሚያሳዬኝ ስብሐት ይሻለኛል፡፡ ጋሽ ፀጋዬ እንደ ዘመንኞቹ ሁሉ በአጉል የእናት አገር ፍቅር የነደደ ሰው ነበር፤ ይሄ መጥፎ ባይሆንም ፍቅር በፉከራ ብቻ መሆኑ ጣጣ እያመጣብን ተቸግረናል፤ አንዳንድ ወንድሞቻችን ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ ጎሰኝነት ማስቀደም ደረጃ ላይ የደረሱት ከዚህ አይነቱ ጭፍን ፍቅር የተነሳ ነው፡፡ የነ ጋሽ ፀጋዬ ‹ኢትዮጵያዬ›› ዘፈን በጎሳ ከመበጣጠስ ሲያድነን አላየንም፡፡
እንዳው ለነገሩስ ቢሆን አገርን በመውደድ ጋሽ ስብሐት ከጋሽ ፀጋዬ ቢበልጥ እንጂ የሚያንስ አይደለም፡፡ እዛው መፅሃፍ ላይ ማዕረጉ በዛብህ እንደፃፉት ‹ጎጃም ላከኝ እና ስለ በላይ ዘለቀ ዘናጭ ፅሁፍ ፅፌ ላምጣ!› የሚል ጀግና ነው፤ ስብሐት፡፡ እነ ጋሽ ፀጋዬም የሼክስፒርን ቲያትሮች እና ግጥሞች ሲተረጉሙልን ኖረዋል፡፡ ስለ ሼክስፒር ስራዎች ማወቅ ባንጠላም በላይ ዘለቀን ጠንቅቆ ማሳወቅ ግን ደምበኛ ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ ‹‹እሳት አመድ ወለደ…..›› የአገርና ባህል ተቆርቋሪ ነን ባዮች ሁሌም የሚዘፍኑት ዘፈን ነው፡፡ አቶ ሚካኤልም ስብሐትን ለመሸርደድ ዘፈነው፡፡ እኔ እንደገባኝ የስብሐት ስራዎች ሁሉ ‹እሳት አመድ ወለደ› የሚል ጭብጥ አላቸው፡፡ ችግሩ ስብሐት በፈጠረው ህልም አይፎክርም፡፡ ሚካኤል በወረደበት ደረጃ ልክ ልምጣለት ብዬ እንጂ እውነት ለመናገር ጋሽ ጸጋዬን እና ስብሐትን ማወዳደር በራሱ ተገቢ ሆኖ አልነበረም፡፡ የኔ አላማ ማነፃፀር ሳይሆን ሁሉም ሰው እንደ ሰው ደካማና ጠንካራ ጎኖች እንዳሉት መናገር ብቻ ነው፡፡

የስብሐት እየሱስ፤ ቡድሃ….ወዘተ….
ስብሐት ግብሩ ከእየሱስ፤ ቡድሃ፤ ጋንዲ….ወዘተ ተቃራኒ ሆኖ ሳለ እነሱን ደጋግሞ ማንሳቱ ለሚካኤል አስገራሚ መሆኑ እኔን ያስገርመኛል፡፡ ስብሐትን እንደ እየሱስ ይሆን ዘንድ መጠበቅ ምን የሚሉት ፍርደ ገምድለነት ነው ጎበዝ? ለምሳሌ ስብሐት የነብዩ መሐመድ ቀንደኛ አድናቂ ነው፤ ሙስሊም መሆን ግን አይጠበቅበትም፡፡ አንድ ሰው ጀግኖችን የሚያደንቀው እሱ ማድረግ ያልቻለውን እነሱ ስለሚያደርጉት ይመስለኛል፡፡ ‹‹ጀግና ማለት ያሸነፈውን የሚያደንቅ ነው›› ይሉ ነበር ወንድ አያቴ፡፡ ስብሐት እሱ ሊሆን የማይችለውን ነገር ሌሎች ሲያደርጉት ሲመለከት ያደንቃል፡፡ እኔም ስብሐትን የማደንቀው እሱ የሚያደርገውን ነገር ማድረግ ስለማልችል ጭምር ነው፡፡ ለምሳሌ ስብሐት ደፋር ነው፤ እኔ ግን ደፋር መሆን የምመኝ ፈሪ ነኝ፤ ታዲያ ስብሐትን ለምን አላድንቀው? ሚካኤል ራሱ መሆን የማይችለውን ነገር ከስብሐት ለምን እንደሚጠብቅ አይገባኝም፡፡ ‹ስብሐትን ከማወቁ በፊት እየሱስን ይመስል ዘንድ ጠብቆት ነበር እንዴ?› ብለህ ጠርጥርም ይለኛል፡፡ ጀግናን ማድነቅ እና ጀግናን መምሰል የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ ስብሐት እነ ማህተመ ጋንዲን ያደንቃል እንጂ እንደነሱ መሆን እፈልጋለሁ አላለም፡፡ ስብሐት ራሱን ከእነኚህ ሰዎች ጋር የሚያነፃፅር ጉረኛም አልነበረም፡፡ ስብሐትን ከጋንዲ ያመሳሰለው ዘነበ ወላ ነው፤ በዘነበ ግነት ስብሐት ስለምን ይወቀሳል?

ድህነት እና ስብሐት
ሚካኤል ስብሐትን ድሃ በመሆኑ ወቅሶታል፡፡ እግረ መንገዱን እኔንም ይውቀሰኝ እንግዲህ፤ እልም ያልኩ ድሃ ነኝና፡፡ ስብሐትን በድህነቱ መውቀስ ጠቅላላ የኢትዮጵያን ህዝብ በእጦቱ እንደ መዘባበት የሚቆጠር ይመስለኛል፡፡ ደግሞ’ኮ ስብሐት ከእግዜር የተሰጠው ሞያ (ድርሰት) ወደ ሐብት ሊመራ የሚያስችል መስመር የለውም፤ ነው ወይስ ድሃ ላለመሆን ስብሐት የመፅሃፍ መሸጫ ሱቅ መክፈት ነበረበት? ስብሐት መክሊቱ ደራሲነት እንጂ የንግድ ጥበብ አለመሆኑን መቼም ስብሐትን ሲከተል ለኖረው ሚካኤል ሽፈራው አልነግረውም፡፡ ስብሐት ሃብታም መሆንን አጥብቆ ባይፈልግም ድህነት ምርጫው እንዳይደለ ግን እርግጠኛ ነኝ፡፡ ስብሐት ድሃ ላለመሆን ማድረግ የነበረበትን ሚካኤል ቢነግረን ጥሩ ነበር፡፡ እዚህ አገር እሳት የላሱ ነጋዴዎችም ድሆች ሲሆኑ ነው የምናውቀው፡፡ ሚካኤል አንድ ህንፃ በወረቀት ላይ ስሎ ብዙ ገንዘብ ቢፈስለት ሁሉም ሰው በቀላሉ ገንዘብ ማግኘት ይችላል ብሎ ካሰበ ተሳስቷል፡፡ የአገራችን የፖለቲካና ኤኮኖሚ ስርዓት ጤነኛ ስላይደለ ገንዘብ የሚፈስባቸው ሰፋፊ ቱቦዎች የሚገኙት እንደ ስብሐት ባሉ ዜጎች አቅጣጫ አለመሆኑን ሚካኤል አለማወቁ አሳሳቢ ነው፡፡

የፈረደባቸው እነ ኢድ፤ ኢጎና ሱፐርኢጎ
መቼም ይቺን የፍሩድን ቀመር በምሳሌ ያላቀረባት ጀማሪ ፈላስፋ የለም፡፡ እንግዲህ በፍሩድ ፍልስፍና የአዕምሮ ተግባራት ትንተና መሰረት ስብሐት ህፃን በሚያሰኘው ኢድ ውስጥ እንደሚመደብ ተነግሯል፡፡ አስደናቂ ነው፡፡ በአገሬው ወግ ሰርግ ደግሶ ትዳር የመሰረተው ስብሃት፤ የአምስት ልጆች አባት ስብሐት፤ የራሱን ኑሮ ራሱን ችሎ መኖር የቻለ ስብሐት፤……ባልዋበት ውለሃል ሲባል መስማት ያስተዛዝባል፡፡ የስብሐትን መልክ አንድ ቀን በአካል በቀሪው የተለያየ ጊዜ ደግሞ በምስል አውቀዋለሁ፤ እኔ የሚታየኝ የሽማግሌ ፊት እንጂ የህፃን ፊት አይደለም፡፡ ሚካኤል የራሱ ኢጎ በፈጠረው ‹ህፃን ስብሐት› ተመርቶ ሰውዬው መደቡ ህፃን ነው ቢለኝ ልንግባባ አንችልም፡፡ ሚካኤል ‹‹…እንደ ስብሐት ያሉ ሰዎችን ፍሮይድ የአዕምሮ ሚዛን መናጋት ናሙና አድርጎ ይወስዳቸዋል፡፡ ፈረሱ ልጓም ሳይገባለት እንደልቡ ሲጋልብ የሚታይባቸው ግለሰቦች በፍሮይድ አገላለፅ (Childhood fixation) በመባል ይታወቃሉ፡፡……›› ይበል እንጂ ስብሐትን ህፃን የሚያስብሉ ተግባራትን አልዘረዘረልንም፡፡ በርግጥ ስብሐት ይቅማል፤ ይሄ ግን ፊክሼስን አይደለም፤ ስብሃት አረቄ ይጠጣል፤ ይሄም ፌክሴሽን አይደለም፤ ስብሐት ልብስ አይቀይርም፤ ይሄም ፊክሴሽን አይደለም፤ ስብሐት ወሲብን በጥሬው ይጠራል፤ ይሄም ፊክሴሽን አይደለም፡፡ ወዘተ….ወዘተ……፡፡ ሚካኤል ስብሐትን በChildhood fixation የፈረጀበት ውሳኔ ማስረጃ የለውም፤ ለዚህ ነው ደረቅ ስም ማጥፋት የሚሆነው፡፡ ስብሐት አንዳንዴ ሲነኩት እንደ ህፃን ቶሎ ቱግ ይላል፤ ምናልባት ይሄን ይሆን ሚካኤል ፊክሴሽን የሚለው? ደግሞ ስብሐት እነ ሚካኤል ሻንጣ ሲያንጠለጥሉ እሱ ፌስታል ይመቸዋል፤ ይሄም ፊክሴሽን ይሆን እንዴ? ሚካኤል ያልቻለበትን ‹ፊክሴሽን› ሲያስረዳ አንድ የሳተው ነገር አለ፤ ይሄውም ሁሉም ሰው የChildhood fixation ተጠቂ መሆኑን ነው፡፡ አንዳንዴ ትልቅ የምንላቸው ሰዎች ያልተጠበቀ የልጅ ስራ ሲሰሩ እናያለን፤ አልፎ አልፎ የሚከሰት የልጅ ባህሪ ሁሉም ዘንድ ይገኛል፡፡ የስብሐት ይበልጣል ከተባለ በስታትስቲክስ ይቀመጥልን፡፡ ከወጣቶች ጋር መዳራት ፊክሴሽን ከተባለ የአዲስ አበባ ሹገር ዳዲ ሁላ የፊክሴሽን ተጠቂ ነው እንበላ!
በአጠቃላይ ሚካኤል ሺፈራው ስብሐትን ሰደበው እንጂ የምናውቃቸውን ደካማ ጎኖቹን እንኳን በቅጡ ሊነግረን አቅም አልነበረውም፡፡ ዘነበ ወላና አለማየሁ ገላጋይ ስብሐትን ‹ቅዱስ› ስላደረጉት ሚዛን መጠበቅ ፈልጎ ከሆነ ስብሐትን በማርከስ መፃፍ አይጠበቅበትም ነበር፡፡ የሚካኤል ችግር የሚጀምረው የስብሃትን ስራዎች ከመተንተን ይልቅ ባህሪው ላይ ማተኮሩ ነው፡፡ ስብሐት ደግ ሆነና ውስጡን ላገኘው ሁሉ አሳየ እንጂ የማንን ቤት ማን ደፍሮ ያውቅ ነበር፡፡ ሚካኤል የስብሐትን ህይወት ስላወቀ አዋርዶ ፃፈው፤ እስኪ ስለ ሐዲስ አለማየሁ አኗኗር አንድ አረፍተ ነገር ይንገረን? ስብሐት ማንም ሊያሳየን የማይችለውን እሱነቱን ከፍቶ ስላስጎበኘን እንደ ጅል ቆጥረን ብንሳለቅበት ጅሎቹ እኛው ነው፡፡ ደግሞም በኢትዮጵያዊነት ግብረገብ ከለላ ያገኙትን መንቀፍ አይቻልም፡፡ ሲጀመር ግብረገብ በሚለው ድፍየና (definition) መች ተስማማንና? ባህል ምንድን ነው? ታሪክ ምንድን ነው? ሌላው ቀርቶ ኢትዮጵያዊነትስ ምንድን ነው? በእነኚህ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ እኮ መግባባት ላይ ያልደረስን ህዝቦች ነን፤ ታዲያ በምን ስሌት ታሪክን፤ ባህልን፤ አገርን ከለላ አድርገን ሌላውን መውቀስ ይቻለናል?
በመጨረሻ፡-
ወንድሜ ሚካኤል ሽፈራው ሆይ - ስብሐትን ከሌላ መዓዘን አየሁት ብለህ የፃፍከውን ነገር እንደገና ብታነበው መዓዘንህን ባታፈርሰው ወይም ባትቀይረው ምን አለ በለኝ፡፡

የአለማየሁ ገላጋይ ስብሐት
የሚካኤል ሽፈራው ‹ልክስክሱ ስብሐት› ለአለማየሁ ገላጋይ ‹ቅዱስ› ነው፡፡ በእውነተኛ ሚዛን ሲሰፍሩት ግን ስብሐት ሁለቱንም አይደለም፡፡ ራሱም ሲለው የኖረው ይህንኑ ነው፡፡ የአለማየሁ ገላጋይ ስብሐትን አለቅጥ የማወደስ አባዜ የመጣው ከሃዘኔታ ይሁን፤ ከይሉኝታ ይሁን፤ ከወዳጅነት ይሁን፤ ከፉገራ ይሁን ግልፅ አይደለም፡፡ ስብሐትን አግዝፎ የመሳል ውጤቱ የሚካኤል ሽፈራውን አርባ ገፅ ስድብ ማስተናገድ ነው፡፡ እዚሁ መልክዓ ስብሐት ላይ አዳም ረታ ምን አለ ‹‹……..ትውስታን አሳስቶ ማቅረብ፤ ትውስታን በርዞ ማቅረብ፤ ትውስታን ሆን ብሎ ማጥፋት በአገራችን ኪነጥበብ መልክዓምድር ላይ ይታያሉ፡፡ ምክንያታቸው ግላዊ፤ ፖለቲካዊ፤ ኤኮኖሚያዊ ወይም ስሜታዊ ሊሆን ይችላል፡፡ በአያያዛችን አሪፍ አንመስልም፡፡…..››
አለማየሁ ይህን መልዕክት በደንብ ቢያጤነው መልካም ነው፡፡ ስብሃትን የያዘበት መንገድ አሪፍ አይደለም፡፡ አንደኛ ስብሐት ይገዝፍ ዘንድ እነ በዓሉ ግርማ በተደጋጋሚ ተደምስሰዋል፡፡ ሁለተኛ ስብሐትን ማግዘፍ በተቃራኒ አቅጣጫ ተመጣጣኝ ሃይሎችን እየፈጠረ ነው፡፡ ከእንዲህ አይነት ጡዘት የሚገኝ ሃይል ውጤቱ ጥፋት ብቻ ነው፡፡ ይሁን እና አለማየሁ ገላጋይ ስብሃትን ለማወደስ 240 ገፅ በፈጀበት ‹ህይወትና ክህሎት› ስራው አሰር ገሰሱን አንፍሰን ፍሬው ሲቀር ባለን ስብሐታዊ ግንዛቤ ላይ መጠነኛ ምስል ስለጨመረልን ብናመሰግነው አይከፋም፡፡ በተረፈ ግን አለማየሁ በተቃራኒው ጠርዝ የቆመ ሌላው (Opposite Copycat) ሚካኤል ሽፈራው ነው፡፡ ‹‹ስብሐት ገብረአግዚአብሔር ህይወትና ክህሎት›› ለንባብ እንደበቃ ጋዜጦች ላይ የተሰጠውን አስተያየት የተጠቀመበትም አልመሰለኝም፡፡ እነ በዓሉ ከስብሐት ተነጥለው ራሳቸውን የቻሉ የፈጠራ ሰዎች ስለሆኑ ስብሐትን በጠራ ቁጥር እነሱ መነካታቸው የማይቀር ከሆነ ችግር አለ ማለት ነው፡፡ በዓሉ “የቀይ ኮከብ ጥሪ” የሚል አርዕስት ከስብሐት ወሰደና ምን ይጠበስ ታዲያ? አለማየሁ አንዳንድ ማስረጃዎቹ ከክር የቀጠኑ በመሆናቸው ራሱን ትዝብት ላይ ሲጥሉት ይታያል፡፡ እዚሁ “መልክዓ ስብሐት” ላይም እንደ ክር የሰለሉ ምሳሌዎችን እያመጣ ስራውን አሳንሶታል፡፡ የፈረደባቸው በዓሉና ዳኛቸው ወርቁ አሁንም ለስብሐት ሲባል ተተችተዋል፡፡ አንዳንዴ ሳስበው አለማየሁ ‹ስብሐትለዓብ› የተሰኘ ሃይማኖት ተከታይ እንጂ የስብሐትን ስራዎች በስርዓቱ ለመመርመር የተነሳ ሃያሲ አይመስለኝም፡፡ ጥረት እና ልፋት በአመክንዮ እና ሀቅ ካልታገዙ ውጤት የላቸውም፤ በተለይ ለሒስ፡፡
አንዳንዴ የአለማየሁ ገላጋይ ወገንተኝነት እየባሰ የመጣው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከሃያሲነት ወደ ፖለቲካ ተንታኝነት በመዞሩ ይሆን? ብዬ መጠርጠርም እፈልጋለሁ፡፡ እንደሚታወቀው በጋዜጠኝነት ስም አለማየሁ በትጋት የሚፋለምበት የተቃውሞ ፖለቲካ ቡድን ሚሳኤል እንጂ ፀረ - ሚሳኤል የለውም፤ ቦምብ ማን ላይ መፈንዳት እንዳለበት እንጂ እንዴት እንደሚፈነዳም አያውቅም፤ ችግር እንጂ መፍትሔ የለውም፡፡ እንግዲህ ወደ ጠላት መተኮስ የለመደ ሰው፣ ደራሲና ሃያሲ ልሁን ሲል ነው ችግር የሚመጣው፡፡
በ”መልክዓ ስብሐት” በአለማየሁ ገላጋይ መጣጥፍ ሃሳቦች ሲጋጩ እንመልከት፡-
ገፅ 241 ላይ የመጀመሪያው ዐረፍተ ነገር ‹‹…ደራሲ እንዴት ያለ ቁመና አለው ብዬ ራሴን የጠየኩበት የመጀመሪያው ገጠመኜ ይሄ ነው፡፡›› ይላል፡፡ አለማየሁ ደራሲን ቁመና ሊሰጠው ወይም መታወቂያ ሊያበጅለት አልሟል ማለት ነው፡፡ (እንደ ስብሐት አጭር እና ጢማም ያልሆንሽ ደራሲ ነኝ ባይ ሁላ ሳያልቅልሽ አይቀርም፤ እንደምንም ብለሽ ቁመትሽን ካላሳጠርሽ እንዲሁም ጢምሽን ካላሳደግሽ፡፡)
የአለማየሁን ፅሁፍ ስትጨርሱ ትክክለኛው የደራሲ ስብዕና የስብሐት አይነት መሆን አለበት ተብሎ መደምደሙን ትታዘባላችሁ፡፡ በዚህ ሂደት ለማንፀሪያነት የቀረቡት ዳኛቸው ወርቁና በዓሉ ግርማ በቀጭን አለንጋ ሲገረፉ እያያችሁ ታዝናላችሁ፡፡ መጀመሪያ ዳኛቸው፤ ስብሐት ራሱን መጣሉ ትክክል እንዳልሆነ ሲመክረው ይታያል፡፡ ቀጥሎ ባለው አንቀፅ ደግሞ ዳኛቸው አራት ኪሎ የሚኖር ጎረቤቱን ለምን ትሰክራለህ? ብሎ መምከሩን በመጥቀስ ይህም ዳኛቸውን የደራሲነት ባህሪ እንደማያሰጠው ይጠቁመናል፡፡ ዳኛቸው ወርቁ ደራሲ ለመባል ሰው መምከር የለበትም ማለት ነው? የበዓሉ ግርማ ሽቅርቅርነትም በአለማየሁ የሂስ ሚዛን ደራሲ አያሰኝም፡፡
ሽቶ ተቀብቶ ውብ ድርሰት መድረስ አይቻልም ማለት ነው? የሚገርመው ነገር አለማየሁ ገላጋይ፤ ደራሲ በተደራሲ ወይም በሌላው ህብረተሰብ ዘንድ ቡትቷም ኮሳሳ ሆኖ መሳሉ ካንገበገበው በኋላ ነው የነበዓሉ ሽቅርቅርነት ደግሞ ለደራሲነት ቁመና የማይመጥን መሆኑን የሚነግረን፡፡ የገዛ ሃሳቦቹን እንዲሁ ያላትማቸዋል፤ ፈርዶባቸው!
በመጨረሻም አለማየሁ ገላጋይን አንድ ጥያቄ ልጠይውና ላብቃ፡-
ውድ ወንድሜ አለማየሁ ገላጋይ - እኔ ወንድምህ ደራሲ መሆን አምሮኝ ነበር - ታዲያ ምን ትመክረኛለህ? እንደ ስብሐት ልኮስስ ወይስ እንደ በዓሉ ልሽቀርቀር?

Published in ጥበብ
Saturday, 17 August 2013 12:03

ለሙያቸው ያላደሩ

የህክምና ባለሙያዎች
የአልትራሳውንድና ላብራቶሪ ምርመራ ለወጪ መሸፈኝያ
የህክምና ሙያ ከሌሎች ሙያዎች ሁሉ እጅግ የከበረና የሰውን ልጅ ክቡር ህይወት ለመታደግ የሚያስችል ሙያ ነው፡፡ የጤና ባለሙያዎቹ ለዚህ እጅግ ለተከበረ ሙያቸው ታማኝ በመሆን ሙያው የሚጠይቀውን ሥነ ምግባር አክብረው ህብረተሰቡን ማገልገል ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህንን ሙያዊ ሥነ ምግባር ጠብቀው በሙያቸውና በዕውቀታቸው ወገኖቻቸውን በመርዳት ተግባር ላይ የተጉ ጥቂት የማይባሉ ሐኪሞች በየሥፍራው ይገኛሉ፡፡ ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ሞያቸውን ለገንዘብ ሸጠው ዓላማቸው ገንዘብ መሰብሰብ ብቻ ሆኖ፣ በተለያዩ የጤና ችግሮች ተይዞ ፈውስ ፍለጋ እነሱ ያሉበት ሥፍራ፣ ደጅ የሚጠናውን ህብረተሰብ ማጉላላትና አግባብ ላልሆኑ ወጪዎች መዳረግ የአንዳንድ ህሊና ቢስ ሐኪሞች ተግባር ነው፡፡
በጤና ተቋማት ውስጥ የሚፈፀሙና የጤና ባለሙያዎች የሥነ ምግባር ጉድለት መገለጫ ናቸው ከሚባሉት ጉዳዮች አንዱን ዛሬ በዚህች አጠር ያለች ፅሁፍ ለመዳሰስ ወደድኩ፡፡ ጉዳዩ በተለይ በግል የጤና ተቋማት ውስጥ በስፋት የሚታየው ህሙማንን አላስፈላጊ ለሆኑ ወጪዎች መዳረግ ነው፡፡ ይሄንንም የሚያደርጉት ለህሙማን ከአስፈላጊው በላይ ምርመራዎችን በማዘዝና በርካታ ገንዘብ እንዲከፍሉ በማድረግ ነው፡፡
በመሠረቱ ለህሙማን የሚደረጉ የጤና ምርመራዎችን አይነትና ምንነት መወሰን የሚችለው የጤና ባለሙያው ብቻ ነው፡፡ ታማሚው ለምርመራ ወደ ጤና ተቋማት ሲሄድ በሽታው በተለያዩ የምርመራ አይነቶች ታውቆለት ለፈውስ የሚሆን መድሃኒት ወይም ህክምናን አገኛለሁ በሚል ተስፋ ነው፡፡ የጤና ባለሙያው ደግሞ ታማሚሙ ስለገጠመው የጤና ችግር ማወቅ የሚችለው በተለያዩ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ መሣሪያዎች ድጋፍ በሚደረጉ ልዩ ልዩ ምርመራዎች ነው፡፡ ሐኪሙ ለበሽተኛው መድሃኒቱን የሚያዘውም በእነዚህ የምርመራ ውጤቶች ላይ ተመርኩዞ መሆኑ አሌ የሚባል ጉዳይ አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ ይህ አሠራር በአንዳንድ ዓላማቸው ከህሙማን ላይ ገንዘብ መሰብሰብ ብቻ በሆነ ህሊናቢስ የጤና ተቋማት ባለቤቶች ዘንድ በተሣሣተ መንገድ ሥራ ላይ ሲውል ማየቱ የተለመደ ጉዳይ ሆኗል፡፡
ለዚህ ፅሁፌ ግብአት የሚሆኑኝን መረጃዎች ለማሰባሰብ በከተማችን ያሉ ስመጥር የግል ሆስፒታሎችንና ክሊኒኮችን በወፍ በረር ቅኝት ተዟዙሬ አይቼአቸው ነበር፡፡ በሆስፒታሎቹ ተቀጥረው የሚሰሩትን የጤና ባለሙያዎች (ዶክተሮች፣ ነርሶችና የላብራቶሪ ባለሙያዎች) ለማነጋገር ጥረት አድርጌአለሁ፡፡ አብዛኛዎቹ የጤና ተቋማቱ ሠራተኞች እነሱ ተቀጥረው በሚሰሩበት ሆስፒታል ውስጥ የሚከናወነውን ከሙያው ሥነ ምግባር ያፈነገጠ ተግባር አውጥተው መናገር አይፈልጉም፡፡ ህክምናውን ለማግኘት ወደ ሆስፒታላቸው የሚመጣው ሰው የሚጠየቀውን ገንዘብ ለማውጣት እስከቻለ ድረስ፣ “ግድ አይሰጠንም፤እሱ ለከፈለው እኛ ምን አገባን” ባይ ናቸው፡፡
የህክምና ሙያ ሥነ ምግባር ጉድለቶች በሙያው ውስጥ ያሉ ሰዎች ሰብዕናን፣ ስለ ሰው ልጆች ያላቸውን አመለካከትና ለሰው ልጆች ያላቸውን ክብር የሚያንፀባርቁ ጉዳዮች ናቸው፡፡ በህክምና ሙያ ውስጥ ያለ ሰው ክቡር ከሆነው የሰው ልጅ ህይወት ይልቅ ገንዘብን የሚያስቀድም ከሆነ ጭንቀቱ ከታካሚው ስለሚገኘው የገንዘብ መጠን እንጂ ለታካሚው ስለሚደረገው የህክምናና እርዳታ ሊሆን አይችልም፡፡ ለዚህ ጉዳይ እንደማሳያ ልጥቀስ፡፡ ሥፍራው እዚሁ አዲስ አበባ አውቶቢስ ተራ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነው፡፡ የሠላሣ ሁለት ዓመት ዕድሜ ያላት ወ/ሮ፤ በአንገቷ ላይ ያለውን እንቅርት ለማስወጣት ወደ ሆስፒታሉ ታመራለች፡፡ ሐኪሙ የታካሚዋን ስሜትና ሁኔታዋን እየጠየቁ በካርዷ ላይ ሲሞሉ ከቆዩና ምርመራቸውን ካጠናቀቁ በኋላ፣ ችግሩ በቀላል ቀዶ ጥገና ሊወገድላት እንደሚችል ነገሯት፡፡ ታካሚዋ በተነገራት እጅግ ተደሰተች፡፡ በሐኪሟ ትእዛዝ መሠረትም ለቀዶ ጥገናው ህክምና ዝግጁ ሆና ትጠባበቅ ጀመር፡፡ ይህ ሁኔታ ግን የሆስፒታሉን ባለቤት እጅግ አበሳጫቸው፣ ህክምናውን ወደ አደረጉላት ዶክተር ዘንድ በመሄድ “ምን እየተደረገ እንደሆነ አስረዳኝ?” ሲሉ ጠየቋቸው፡፡ ዶክተሩ ግራ ተጋቡ፡፡ “ምን እየተደረገ ነው?” መልሰው ጠየቋቸው፡፡ “ከደቂቃዎች በፊት ለመረመርካት ታካሚ እንዴት የአልትራሳውንድና የላብራቶሪ ምርመራ ሣታዝላት ቀረህ?” አሏቸው፡፡
ዶክተሩ ምርመራው አስፈላጊ እንዳልነበረና ህመምተኛዋ የሚያስፈልጋት ቀላል ቀዶ ህክምና ብቻ መሆኑን ገለፁላቸው፡፡ ይህ ምላሽ ግን የሆስፒታሉ ባለቤት በሆኑት ዶክተር ዘንድ ፈፅሞ ተቀባይነት አልነበረውም፡፡ “ታዲያ ይህ ሁሉ ወጪ በምን ሊሸፈን ነው? አንተ ተረኛ በሆንክ ጊዜ ላብራቶሪውና አልትራሳውንድ ክፍሉ ሥራ ፈቶ ይውላል፡፡ እንደ ሌሎቹ ዶክተሮች ሁሉን ነገር ቶሎ ቶሎ እዘዝ እንጂ” ማሳሰቢያውን ነግረዋቸው ሄዱ፡፡ “ምን ብዬ እንደምመልስለት ሁሉ ጠፋኝ፣ወደ ህክምና ሙያ ስገባ ህመምተኛዬን ልንከባከብ፣ ሚስጢሩን ልጠብቅለት፣ ያለ አግባብ ላላጉላላው የገባሁት ቃል ሁሉ ገደል ሲገባ ታየኝ፡፡ ከዚህ ሰውዬ ጋር አብሬ መዝለቅ እንደማልችል በመረዳቴም ሥራዬን ለቅቄ ወጣሁ፡፡ የሚገርምሽ ነገር ግን ይህ ሁኔታ በሌሎችም የግል ጤና ተቋማት ውስጥ የገጠመኝ መሆኑ ነው፡፡”
ይሄን ያጫወቱኝ ዶክተር ታረቀኝ ሀብታሙ የተባሉ የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ናቸው፡፡ ለዚህ ጉዳይ ማሳያ ይሆናል ያልኩት ሌላ ታሪክ የተፈፀመው ከጥቂት ዓመታት በፊት በኮሪያ ሆስፒታል ውስጥ ነው፡፡ አንድ የከባድ መኪና መካኒክ፣ በሥራ ላይ እያለ የጭነት መኪናው ጋቢን ድንገት እላዩ ላይ ይወድቅበታል፡፡ አደጋው እጅግ ዘግናኝና አሳዛኝ ነበር፡፡ ሆኖም የሰውየው ነፍስ አልወጣችም፡፡ እንደምንም አንስተው ወደ ኮሪያ ሆስፒታል ይዘውት በረሩ፡፡ ከሆስፒታሉ ሲደርስ ትንፋሹ ያለ አይመስልም ነበር፡፡
በአስቸኳይ ወደ ኦፕሬሽን ክፍል እንዲገባ ታዘዘ፡፡ የቤተሰቦቹ ሃሳብ በሁለት ተከፍሏል፣ ገሚሱ ተስፋ እንደሌለው በመገመት ወደ ቤት ይዘውት ለመሄድ ሃሳብ ሲያቀርቡ፣ ገሚሶቹ ደግሞ የእግዚአብሔር ነገር ምን ይታወቃል ይሞከር አሉና ወደ ቀዶ ጥገናው ክፍል እንዲገባ ፈቀዱ፡፡ ቅድሚያ 10ሺህ ብር እንዲያሲዙ ተጠይቀው አስያዙ፡፡ ሰዓታት ነጐዱ፣ ሰውየው ግን ከቀዶ ጥገናው ክፍል አልወጣም፡፡ ከበድ ያለ የቀዶ ህክምና እየተደረገለት እንደሆነ የጠረጠሩት ቤተሰቦቹ፣ እዛው ሆስፒታሉ ውስጥ ሲንቆራጠጡ ቆዩ፡፡ ከሰዓታት በኋላ ሰውየውን ማዳን እንዳልቻሉና ህይወቱ እንዳለፈች ተነገራቸው፡፡ ሁኔታው እጅግ አሳዘናቸው፡፡ አስከሬኑን ለማውጣትና የከፈሉትን ገንዘብ ለማስመለስ ጥያቄ ያቀረቡት የሟች ቤተሰቦች፣ ካስያዙት ገንዘብ ተመላሽ የተደረገላቸዉ ከአንድ ሺህ ብር የማይበልጥ ገንዘብ ነበር፡፡ አገር ይያዝ አሉ- ቤተሰቦች፡፡
“አስከሬኑንም አናወጣም፣ ከሃላፊዎች ጋር እንነጋገራለን” አሉ፡፡ ትችላላችሁ ተባሉ፡፡ ጊዜው መሸ፡፡ ኃላፊዎቹን አነጋግረው አስከሬኑን ጠዋት ለማውጣት ይወስኑና ይሄዳሉ፡፡ በማግስቱ ኃላፊ ከተባሉት ሰዎች ጋር ቢነጋገሩም ምንም መፍትሔ አልተገኘም፡፡ ጭራሽ አስከሬኑን ሲረከቡ ለተጨማሪ አንድ ቀን በሆስፒታሉ ላደረበት 300 ብር እንዲከፍሉ ተደረጉ፡፡
ሌላው ገጠመኝ በቤቴል ቲቺንግ ሆስፒታል ውስጥ የደረሰ ነው፡፡ ሴትየዋ በሆስፒታሉ አልጋ ይዛ ስትታከም ትቆይና ህክምናዋን አጠናቅቃ፣ ከሆስፒታሉ ለመውጣት ባለቤቷ ሂሣብ ያሰራል፡፡ በዚህ ወቅትም ያስያዙት ገንዘብ አልቆ ተጨማሪ 2ሺህ ብር መክፈል እንደሚጠበቅባቸው ይነገረዋል፡፡ ባል ጉዳዩ አስደነገጠው፡፡ በእጁ ገንዘብ እንደሌለው ተናገረ፡፡ “ሄደህ ማምጣት ትችላለህ ፤እሷ ግን ከዚህ መውጣት አትችልም” አሉት፡፡ አማራጭ አልነበረውና ህመምተኛ ሚስቱን በመያዣነት አስይዞ፤ አለብህ የተባለውን ገንዘብ ለማምጣት ወደ ቤቱ ሄደ፡፡ ቤቱ ከአዲስ አበባ ውጪ አሰላ የሚባል ከተማ ውስጥ በመሆኑ በዕለቱ መመለስ አልቻለም፡፡ አደረና በማግስቱ ተጨማሪ የአንድ ቀን ሂሣቡን ከፍሎ ሚስቱን ከታገተችበት አስለቅቆ ወጣ፡፡
እንዲህ እንዲህ ያሉ አሣዛኝና ከህክምናው ሥነ ምግባር ውጪ የሆኑ ታሪኮችን መስማት አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ይህ የሙያውን ስነ ምግባር ጥሰው በወገኖቻቸው ላይ በደል የሚፈፅሙ ህሊና ቢስ የጤና ባለሙያዎች ተግባር እንጂ በህክምና ሙያ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች ሁሉ ተግባር እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ የህመምተኛቸውን አቅም ተረድተው ከኪሣቸው ገንዘብ እየከፈሉ ምርመራና ህክምና የሚያደርጉ፣ የህመምተኛቸውን ችግር ለመስማት ጆሮአቸውን የሚሰጡ፣ አላስፈላጊ ከሆኑ ወጪዎች ህመምተኛቸውን የሚጠብቁ በርካታ የህክምና ባለሙያዎች እዚሁ አገራችን ውስጥ አሉ፡፡ እነዚህ ዓይነቶቹ ምስጋናና አድናቆት ይገባቸዋል፡፡ እነዛኞቹ ደግሞ ወደ ልቦናቸው ተመልሰው ወገኖቻቸውን በታማኝነት ለማገልገል እንዲችሉ ምክርና ተግሳፅ፡፡

Published in ዋናው ጤና

ጥናት በተደረገባቸው የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ እና የመሰናዶ ትምህርት ተከታታይ ሴቶች ዘንድ ፡-
ወሲባዊ ድርጊት ለመጀመሪያ ጊዜ ሲፈጸም እርግዝና ሊከሰት እንደሚችል የሚያውቁ ተማሪዎች 8.2 ኀናቸው፡፡
ያልተፈለገ እርግዝናን ለመከላከል መወሰድ የሚገባቸውን መከላከያዎች በሚመለከትም ትክክለኛው መረጃ ያላቸው 5.6 ኀ ብቻ ናቸው፡፡
Yohannes A. (Mekelle University, College of Health Sciences, Department of public health)
ከላይ የተመለከተውን መረጃ ያገኘነው በሰሜን ኢትጵያ በመቀሌ የተደረገ ጥናት በአቶ ዮሐንስ ከመቀሌ ዩኒቨርስቲ አማካኝነት የቀረበ ነው፡፡ የስነተዋልዶ ናንና ያልተፈለገ እርግዝናን ለመከላከል በሚያስችል ሁኔታ እውቀትን ለመገብየት ወጣቶች ከቤተሰባቸወና ኝጉዋደኞቻቸው ጋር መምከር አለባቸው ሲሉ ያንሄዱትን የዳሰሳ ስራራ ወደ አማርኛ በመመለስ ለንባብ አቅርበናል ፡ ይህ ጥናት ከሚያሳየው ውጤት በመነሳት አንባቢዎች የየራራሳቸውን እርምጃ እንደሚወስዱ አምዱ ይማመናል፡፡
እንደአቶ ጥናቱ መረጃ አለምአቀፋዊውን የህዝብ ቁጥር 1.2 ቢሊዮን ያህሉን የሚጋሩት በእድሜያቸው ከ15-24 የሚደርሱ ወጣቶች ናቸው፡፡..፣ዛጨ.. ወጣቶች በአለም ላይ በተለያዩ የህይወት አጋጣሚዎች የሚፈተኑ ከመሆናቸው ጋር በተያያዘም ለተለያዩ የስነ ተዋልዶ ና ችግሮችና ላልተፈለገ እርግዝናም ለመጋለጥ ቅርብ ናቸው፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ በየአመቱ ከሚኖሩ ወሊዶች 11 %ዴ..ክኽ በእድሜያቸው ከ15-19 አመት የሚሆኑ ሴት ልጆች የሚወልዱት ሲሆን ይህም ወደ 95 %የሚሆነው በታዳጊ አገሮች ውስጥ የሚከሰት ነው፡፡
በሌላም በኩል ወደ 2.5/ ሚሊዮን የሚሆነው ማለትም በታዳጊ አገሮች ውስጥ የሚኖረው ደህንነቱ ያልተጠበቀ ውርጃ በእድሜያቸው ከ20/አመት በታች በሆኑ ሴት ልጆች የሚፈጸም ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በእድሜያቸው ልጅ የሆኑ ሴቶች እርግዝና በሚያጋጥማቸው ጊዜ ከእርግዝናው ጋር በተገናኛ ለሚፈጠር ሌላ የጤና ችግርም እንደሚጋለጡ እና የጽንስ መቋረጥ ሊገጥማቸው እንደሚችል እሙን ነው፡፡ ቀጥሎ የተመለከቱትን ነጥቦች ጥናቱ እንደማሳያ ..ፐቭቨዩቓም፡፡
የልጅነት ባህርይ -
ሴት ልጆች የልጅነት ባህርይን ባልተላቀቁበት እድሜያቸው ለወሲብ ድርጊት ቢጋለጡ እርግዝና ሊከተል ይችላል፡፡ ልጅን መውለድ አብሮት የሚመጣ ኃላፊነት እንደሚሆንም ግልጽ ነው፡፡ ልጅን ተንከባክቦ ናውን ብቆ ትን በተገቢው አጥብቶ ማሳደግና ሙሉ በሙሉ ንነቱን መንከባከብ ፣ እድገቱን መከታተል የቤተሰብ በተለይም ሁልጊዜም ለልጁ ቅርብ ወደሆነችው እናት ያዘነብላል። ይህንን ኃላ ፊነት ለመወጣት ዝግጁ ባልሆኑበት እድሜ እርግዝና ሲከሰት ልጆቹ በግልጽም ይሁን በድብቅ ጽንሱን ወደማቋረጥ እንደሚያዘነብሉ እሙን ነው፡፡ ለተፈጠረው ችግር መፍትሔ የሻቱ መስሎአቸው በሚወስዱት እርምጃ ወይንም ጥንቃቄ በጎደለው መንገድ ወሲብ በመፈጸማቸው እና ጥንቃቄ የጎደለው ጽንስ ማቋረጥን ቢተገብሩ እና ለስነተዋልዶ ና ጉደለት ቢጋለጡ ከቤተሰብ እና ኝጉዋደኞቻቸው ድብቅ በሆነ መንገድ ጉዳት ላይ ሊወድቁ የሚችሉበት አጋጣሚ ይፈጠራራል፡፡
ሴት ሕጻናቱ በእንደዚህ ያለው አጋጣሚ በትምህርት ከሌሎች ጉዋደኞቻቸው ዝቅ ወደ ማለት ስለሚያዘነብሉ ተስፋ ወደመ ቁረጥ እና እራራሳቸውንም ወደመጥላት ሊደርሱ ይችላሉ፡፡ ምናልባትም ትምህርታቸውንም አቋርጠው ልጁን እንዲወልዱ እንኩዋን ቢደረግ ፈቃደኛ ሆነው እንደእናት ተንከባክቦ የማሳደግ ጥረቱ እምብዛም አይታይም፡፡
በስነተዋልዶ ና ላይ መነጋገር፡-
ጥናቱ እንደሚጠቁመው በኢትዮጵያም ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ደረጃ በስነተዋልዶ አካላት ላይ የተመሰረተ ንግግር ወይም ውይይት ማድረግ እንደነውር የሚቆጠርበት አጋጣሚ አለ፡፡ በስነተዋልዶ አካላት ላይ መነጋገር ካልተቻለ ደግሞ ሊደርስ በሚችለው የጤና ጉዳይ እና ሊደ ረግ ስለሚገባው ጥንቃቄ መነጋገር አስቸጋሪ ይሆናል። በስነተዋልዶ አካላት ና ላይ በግልጽ መነጋገር ማለት ግን የጤና ችግር ከመፈጠሩ አስቀድሞ መፍትሔ ለመሻት የሚያስችል እው ቀትን ለማግኘት የሚረዳ እና ከራራስም አልፎ ለሌሎችም መምከር የሚያስችል ንቃተ ሕሊናን ማዳበር የሚያስችል ነው፡፡
ሴቶች በስነተዋልዶ ና ንቃተ ሕሊናቸው የመዳበሩ አሰፈላጊነት ከሚታይባቸው ነጥቦች መካከለ የቤተሰብ እቅድ ዘዴ ወይንም ያልተፈለገ እርግዝናን መከላከል አንዱ ነው፡፡ ሴቶች ልጆችም ሆኑ የትዳር ወይንም የፍቅር ጉዋደኞቻቸው ልጅ መውለድ የሚቻልበትን ጊዜ አስቀድሞ በመመካከር ወስነው ልጅ መውለድ የሚገባቸው ሲሆን ከዚያ ውጭ ከሆነ ግን በግልጽ ካለመነጋገር ወይንም በመተፋፈር አላስፈላጊ ለሆኑ ችግሮች ሊጋለጡ ይችላሉ። ከነዚህም መካከል፡-
ላልተፈለገ እርግዝና መጋለጥ፣
ጥንቃቄ የጎደለው ጽንስ ማቋረጥ፣
በልጅነት ልጅ መውለድ፣
የልጅነት ባህርይ ስለሚኖር ወላጅነትን የመቀበል ችግር፣
ትምህርትን ማቋረጥ እና ሕይወትንም እስከማጣት ለሚያደርስ ችግር ሊጋለጡ ይችላሉ፡፡
ያልተፈለገ እርግዝናን ለመከላከል በሚያስችሉ ነጥቦች ላይ የተለያዩ ጥናቶች በአገራራችን መካሄዳቸው እውን ቢሆንም በአብዛኛው በድርጊት ላይ ያተኮሩ እና በአፋጣኝ የእርግዝና መከ ላከያ ወይንም Emergency contraceptive ላይ ያተኮሩ ናቸው ፡ እስከአሁን ድረስ በተደረጉ ጥና ቶች በወላጆች እና በጉዋደኛሞች መካከል በስነተዋልዶ ና ጉዳይ ላይ በተለይም የእርግዝና መከ ላከያን በሚመለከት ሊኖር የሚገባውን የእርስ በእርስ ውይይት በሚመለከት ምንም የተደረገ ጥናት የለም ማለት ይቻላል ይላል ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የቀረበው ጥናት፡፡
ይህንን ርእሰ ጉዳይ በመቀሌ ከ20/ ሺህ በላይ በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ እና በመሰናዶ ትምህርት በመማር ላይ ባሉ ተማሪዎች አካባቢ ጥናት የተደረገ ሲሆን ከእነዚህ ተማሪዎች መካከል 11/አስራራ አንድሺህ የሚሆኑት ሴት ተማሪዎች እንደሆኑ ጥናቱ ይጠቁማል፡፡ ከእነዚህም መካከል ለጥናቱ በናሙናነት የተመረጡት ከየትምህርት ቤቱ በአጠቃላይ ወደ 845/የሚሆኑ ሴት ተማሪዎች ናቸው። በቤተሰብና በጉዋደኛሞች መካከል ሊደረግ ስለሚገባው ግልጽ ውይይት በጥናቱ ወቅት ከታዩ አንዳንድ ለሴት ተማሪዎቹ ምቹ ያልሆኑ ነጥቦች መካከል፡-
የትምህርት እና የማህበራራዊ አኑዋኑዋር፣
የወላጆች በትክክል ከተማሪዎች ጋር አለመናበብ፣
በተማሪዎቹ መካከል ያለ ወሲባዊ ባህርይና የስነተዋልዶ ና ሁኔታ መለያየት፣
በተለያዩ መገናኛ ብዙሀን የሚተላለፉ መልእክቶች ፣
ከወላጆች ወይንም ከጉዋደኞች ጋር በወሲብና ስነተዋልዶ አካል ዙሪያ ውይይት አለማድረግ የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡
በጥናቱ ከታየው ውጤት መረዳት እንደሚቻለው ከተሳታፊዎቹ ውስጥ አንድ አምስተኛ (171)የሚሆኑት አስቀድሞኣኽ፣ኽጋ የወሲብ ጉዋደኛ ያላቸው ሲሆን ሶስት አራራተኛው 127ግን በትምህርት ቤት ውስጥ ጥናት ከመሳሰለው ጋር በተያያዘ የወሲብ ጉዋደኛ እንዳፈሩ ታውቆአል፡፡ ወሲብ በመፈጸም ረገድም ገሚሶቹ አስቀድሞኣኽ፣ኽጋ የጀመሩ ሲሆን አንዳንዶች ደግሞ በትምህርት ቤት ለጥናት በሚል ሰበብ ካፈሩዋቸው ጉዋደኞቻቸው ጋር መጀመራራቸውን መስክረዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ወደ 15 % የሚሆኑት አስቀድሞኣኽ፣ኽጋ አርግዘው እንደሚያውቁ ከነዚህም ወደ 90 % የሚሆኑት ውርጃን እንዳከናወኑ ገልጸዋል፡፡
ያልተፈለገ እርግዝናን በተመለከተ ተማሪዎቹ ሲጠየቁ የመለሱት በእርግጥ ቢያንስ ስለ አንድ አይነት የመከላከያ ዘዴ ሰምተው የሚያውቁ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ያልተፈለገ እርግዝናን ለመከላከል ያለው መንገድ የወንዶች ኮንዶም ብቻ አንደሆነ የሚያውቁ መሆኑን ለጥያቄው መልስ ሰጥተዋል፡፡ በጥናቱ ከተሳተፉት መካከል ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያን በመርፌ ወይንም በእንክብል መልክ እንደሚሰጥ የሰሙ መሆኑን የገለጹ ያሉ ቢሆንም ወደ 80 %ኛትሽ ሆኑት አገልግሎቱ የሚሰጠው ከአንድ ስፍራራ ብቻ መሆኑ እንደሚያውቁ ገልጸዋል፡፡ ወሲባዊ ድርጊት ለመጀመሪያ ጊዜ ሲፈጸም እርግዝና ሊከሰት እንደሚችል የሚያውቁ ተማሪዎች 8.2 % ናቸው፡፡ ያልተፈለገ እርግዝናን ለመከላከል መወሰድ የሚገባቸውን መከላከያዎች በሚመለከትም ትክክለኛው መረጃ ያላቸው 5.6 %ብቻ ነበሩ፡፡
በአጠቃላይ በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ እና በመሰናዶ ትምህርት ላይ በነበሩ ሴት ተማሪዎች ላይ በተደረገው ጥናት ያልተፈለገ እርግዝናን መከላልን በሚመለከት የነበራራቸው ግንዛቤ እጅግ አሳሳቢ ሆኖ ነው የተገኘው፡፡ በጥናቱ ለናሙና ከተወሰዱት ተማሪዎች መካከል ስለሁኔታው በቂ እውቀት ያላቸውና እራራሳቸውን ካልተፈለገ እርግዝና መከላከል የሚችሉት በጣም ጥቂት ሆነው ነወ የተገኙት ምንም እንኩዋን መልእክቱ በተለያዩ መገናኛ ብዙሀን የሚተላለፍ ቢሆንም ቀጣይነት ባለው መንገድ እና ንቃተ ሕሊናን በሚያዳብር መልኩ መሆኑ አጠራራጣሪ ከመሆኑም ባሻገር መልእክቱ ምን ያህል ሴት ተማሪዎቹ ጋር ደርሶአል የሚለውን ለመገመት አስቸጋሪ ነው፡፡
ጥናቱ በማጠቃለያው ያመላከተው በመላ ሀገሪቱ ባሉ ወጣቶች ዘንድ ያለው ሁኔታ በቀጣይነት ሊጠና እንደሚገባውና እንዲሁም ቤተሰብ ለልጆቹ ቅርብ በመሆን በስነተዋልዶ አካላት ጉዳይ ላይ ግልጽ ውይይት ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ትምህርት ቤቶችም በጉዋደኛሞች መካከል ለሚያስፈልገው የእርስ በእርስ ውይይት ምቹ ሁኔታን መፍጠር ..ጭፐቨዩቓም፡፡ ወጣቶችም የሚገጥማቸውን ማንኛውንም ነገር በቅርብ ካለ ጉዋደኛ እንዲሁም ከቤተሰብ ጋር በግልጽ መወያየትን እንዲያምኑና እንዲተገብሩ ያስፈልጋል፡፡

Published in ላንተና ላንቺ

ግብጽን ከሠላሳ አመት በላይ ከብረት በጠነከረ እጃቸው ሰጥ ለጥ አድርገው የገዙት ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ፤በቱኒዚያ የተቀሰቀሰው ህዝባዊ አብዮት ፕሬዚዳንቱን ዜን አብዲን ቤንአሊን አገር ጥለው እንዲሰደዱ እንዳደረጋቸው ዋነኛው የደህንነት ምኒስትራቸው ሲያስረዷቸው፤ “ምስኪን ቤንአሊ! ለጥቂት አመፀኛ ጐረምሶች ብሎ አገሩን ጥሎ ተሰደደ?” በማለት ማሾፋቸውን፤ግብጻውያን በተራቸው እያሾፉ ተናግረው ነበር፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ ፕሬዚዳንት ሙባረክ በቱኒዚያው ፕሬዚዳት ከአገር ጥሎ መጥፋት ቢያሾፉ አይፈረድባቸውም ነበር፡፡ ለምን ቢባል--- ከሠላሳ አመት በላይ በዘለቀው አምባገነናዊ አገዛዛቸው፣ በህዝባቸው ላይ ምን አይነት አስተሳሠብና ስሜት መፍጠር እንደቻሉ በሚገባ ያውቁ ስለነበር ነው፡፡
ፕሬዚዳንት አንዋር አልሳዳት በ1981 ዓ.ም በካይሮ አደባባይ ወታደራዊ ትርኢት እየተከታተሉ እንዳለ የኢስላሚክ ጅሀድ አባላት በሆኑ ጽንፈኛ ሙስሊም ታጣቂዎች በጠራራ ፀሀይ በጥይት ተደብድበው ከተገደሉ በኋላ በእግራቸው የተተኩት ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ፣ ከሁሉም አስቀድመው የወሰዱት እርምጃ ስልጣናቸዉን ማደላደል ነበር፡፡ ይህንንም ለማድረግ የመጀመሪያው ስራ የስልጣናቸውን ተቀናቃኞች ቀድሞ መጥረግ ነበር፡፡ በዚህ የተነሳም የመጀመሪያውን እርምጃ ለመውሰድ የቅጣት ሰይፋቸውን የመዘዙት ጽንፈኛ ሙስሊም ድርጅቶች ናቸው በተባሉት በኢስላሚክ ጅሀድና በሙስሊም ወንድማማቾች የፖለቲካ ድርጅቶችና አባሎቻቸው ላይ ነበር፡፡
ስልጣን በያዙ ሶስት አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥም ኢስላሚክ ጅሀድ የተባለውን የፖለቲካ ድርጅት ከነመላ አባላቶቹ ጨርሶ ያልነበረ ያህል ድምጥማጡን ሲያጠፉት፣ሙስሊም ወንድማማቾች የተሠኘውን እስላማዊ የፖለቲካ ድርጅት ደግሞ አከርካሪውን በመስበር፣ ከግድያና ከወህኒ ቤት እስር ያመለጡ አባላቶቹ ህቡዕ እንዲገቡ አስገደዷቸው፡፡ ከዚህ በኋላ በመጡት ጥቂት አመታት ውስጥ ደግሞ ፊታቸውን በህዝቡ ዘንድ ባላቸው ተቀባይነት ቀላል ሚዛን ናቸው ወደተባሉት ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች በማዞር፣በግብጽ የፖለቲካ መድረክ ላይ ቅንጣት ታክል የእግር መትከያ ቦታ እንዳይኖራቸው በማድረግ ከፖለቲካ ጨዋታው ጨርሰው እንዲወጡ አደረጓቸው፡፡
የፕሬዚዳንት አንዋር ሳዳትን አስረኛ የሙት አመት፣ የእርሳቸውን ደግሞ አስረኛ የፕሬዚዳንትነት አመት በመስከረም 1991 ዓ.ም ሲያከብሩ፣ በመላዋ ግብጽ ውስጥ የነበረው አንድ ፓርቲና ምክትል ፕሬዚዳንት እንኳ ለመሾም ፈቃደኛ ያልሆነ አንድ አምባገነን መሪ ብቻ ነበር፡፡ የፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ ፓርቲና ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ፡፡ ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ፣ ይህንን ካደረጉና ስልጣናቸውን በአስተማማኝ ሁኔታ ካረጋገጡ በኋላም እንኳ የብረት መዳፋቸውን በህዝባቸው ላይ ላላ ለማድረግ ጨርሶ ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡ ቀጣዮቹን ሀያ አመታት ያሳለፉትም ስልጣናቸውን ከእለት እለት ፍፁም የለየለት አምባገነን በማድረግና በህዝባቸው ልብና አዕምሮ ውስጥ ልብ የሚያቆምና አጥንት የሚያጐብጥ ፍርሀት በመትከል ነበር፡፡
ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ፣ ከሠላሳ አመታት በላይ የዘለቀውን ፍፁም አምባገነናዊ አገዛዛቸውን በምድረ ግብጽ መመስረት የቻሉት እንደው እንደዘበት አልነበረም፡፡ የዚያ ምህረት የለሽ የብረት መዳፋቸው ልዩ ጡንቻዎች የደህንነት ሀይላቸውና በፊልድ ማርሻል ሞሀመድ ታንታዊ ፊት አውራሪነት የሚመራው የጦር ሀይሉ ከጎናቸው ነበሩ፡፡ ህዝባዊውን አመጽ መቋቋም ተስኗቸው የቱኒዚያው ፕሬዚዳንት ሀገራቸውን ለቀው የመሰደዳቸው ዜና ሲነገራቸው፣ ያሾፉትም በሌላ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ በእሳቸው ቁጥጥር ስር ባለው የደህንነትና የጦር ሀይላቸው በሙሉ ልብ በመተማመናቸው ነበር፡፡
በእርግጥም ፕሬዚዳንት ሙባረክ የስልጣን ተቀናቃኞቻቸውን ሁሉ፣ እንኳን በምድረ ግብጽ በመላው የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ሳይቀር እገቡበት እየገባ፣ አንገታቸውን በመቀንጠስ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል በፍፁም ታማኝነት ለሠላሳ አንድ አመታት ባገለገሏቸው የደህንነትና የጦር ሀይሉ በመተማመን ነገር አለሙን ሁሉ ጥለውት ነበር፡፡ ከቱኒዝያ የተነሳው የአረብ ህዝባዊ አብዮት የሰደድ እሳቱ ድንገት ካይሮ ታህሪር አደባባይ ከች ብሎ ባልጠበቁት ጊዜና ባልታጠቁበት ሁኔታ የለበለባቸውም በዚህ ምክንያት ነበር፡፡ ግብፃውያን የአምባገነኑን የፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክን ጨቋኝና አፋኝ አገዛዝ ለመገርሰስ ያካሄዱት አብዮት ሁለት ነበር፡፡ ሁለተኛውንና ዋናውን አብዮት ታህሪር አደባባይ በመውጣት ከማካሄዳቸው በፊት የመጀመሪያውን አብዮት ያካሄዱት ለሰላሳ አንድ አመታት ክፉኛ ተጭኗቸው የነበረውን ከፍተኛ ፍርሀት በማሸነፍ ነበር፡፡ ግብፃውያን ፕሬዚዳንት ሙባረክን ከስልጣናቸው ነቅሎ ለማባረር ባካሄዱት አብዮት ክፉኛ ፈርተውት የነበረው የፕሬዚዳንቱ ቀኝ እጅ የነበረውን የግብጽን ጦር ሀይል ነበር፡፡ በተግባር የሆነው ግን የተገላቢጦሽ ነበር፡፡ ፕሬዚዳንቱን በመደገፍ አብዮቱን ሊያከሽፍ ይችላል ተብሎ በከፍተኛ ሁኔታ ተፈርቶ የነበረው ጦር ሀይል፣ባልተገመተና ባልተጠበቀ ሁኔታ ወገንተኝነቱን ለህዝብ ማሳየት ቻለ፡፡
ፕሬዚዳንት ሙባረክም እስከመጨረሻው ድረስ የቻሉትን ያህል ቢፍጨረጨሩም በህዝባዊው አብዮት ሰደድ እሳት ከመለብለብ ራሳቸውንና አገዛዛቸውን ማዳን ሳይችሉ ቀሩ፡፡ በቱኒዚያው ፕሬዚዳንት ካገር ለቆ መጥፋት ያሾፉት ሙባረክም ግብጽን ለቀው ለመውጣት ሳይችሉ ቀርተው፣ተቀናቃኝና ተቃዋሚዎቸቸውን ሲያጉሩበት በነበረው ወህኒ ቤት፣ የማታ ማታ እርሳቸውም የእድሜ ልክ እስር ተበይኖባቸው ለመታጐር በቁ፡፡ የግብጽ ህዝባዊ አብዮት፣ ከአምባገነኑ የሙባረክ አገዛዝ ነፃ ያወጣው የግብጽን ህዝብ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ድርጅቶችንም ጭምር ነው፡፡ ይህ ህዝባዊ አብዮት በተለይ ከሠላሳ አመታት በላይ ቁም ስቅሉን ላየው ሙስሊም ወንድማማቾች የፖለቲካ ድርጅትና ደጋፊዎቹ በእጅጉ የተለየ ነበር፡፡ የግብጽ ህዝባዊ አብዮት የሙስሊም ወንድማማቾች ድርጅትን ነፃ ማውጣት ብቻ ሳይሆን የአመራር ወንበሩንና በትረ ስልጣኑን ነበር ያስጨበጠው፡፡ ህዝባዊ አብዮቱን ተከትሎ በምድረ ግብጽ ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው ህዝባዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ስልጣኑን መቆናጠጥ የቻለው የሙስሊም ወንድማማቾች ድርጅት ነው፡፡
በግብጽ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው ምርጫ፣ በህዝብ ድምጽ ተመርጠው ስልጣን መያዝ የቻሉት ፕሬዚዳት ሞሀመድ ሙርሲም የሙስሊም ወንማማማቾች ድርጅት ያቀረባቸው ናቸው፡፡ በምርጫው በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች ከፍተኛ ፉክክር ቢያደርጉም፣ ካለው የደጋፊ ቁጥርና ተቀባይነት አንፃር የሙስሊም ወንድማማቾች እንደሚያሸንፍ አስቀድሞም ቢሆን ተገምቶ ስለነበር አንድም ግብፃዊ በውጤቱ አልተገረመም ነበር፡፡ አስገራሚው ነገር ከምርጫው በኋላ ለአዲሱ ተመራጭ ፕሬዚዳንት ሞሀመድ ሙርሲ ህዝቡ የሰጣቸው ማሳሰቢያ ነበር፡፡ ህዝቡ ለፕሬዚዳንት ሞርሲ የሰጣቸው ማሳሰቢያ፣ ደምና ህይወት ከፍለው እውን ያደረጉት አብዮት ግቡን እንዲመታ፣ ቃል የገቡትን ሁሉ በተግባር ለመተርጐም የአንድ አመት ጊዜ እንደሠጧቸው፣ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ውጤት ማምጣት ካልቻሉ ግን በምርጫ የሠጧቸውን ስልጣን መልሰው እንደሚነጥቋቸው የሚያስጠነቅቅ ነበር፡፡ ፕሬዚዳንት ሞርሲም “ግዴላችሁም በእኔ ይሁንባችሁ” ብለው ተጨማሪ ቃል ገብተው ነበር፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ ፕሬዚዳንት ሞሀመድ ሞርሲ በምርጫው ወቅት የገቡትን ቃልና ህዝቡ የሰጣቸውንም ማሳሰቢያ ጨርሰው የረሱት ምናልባትም ሆን ብለው ችላ ያሉት በብርሀን ፍጥነት ነበር፡፡ ግብጽን ለመምራት ቃለ መሀላ ፈጽመው የፕሬዚዳንትነት ስልጣኑን ከተረከቡ በኋላ፣ በማግስቱ ራሳቸውን በዋናነት የጠመዱት የጦር ሀይሉን አንጋፋ መሪዎች በጡረታ በማሰናበት፣ የእሳቸው ደጋፊ የሆኑ ከፍተኛ መኮንኖችን መተካት፣ የግብጽን ጠቅላይ አቃቤ ህግና ፍርድ ቤቶችን በደጋፊዎቻቸው መሙላት፣በተለይ ደግሞ የግብጽን ህገመንግስት ፈላጭ ቆራጭ ስልጣን እንዲኖራቸው አድርገው በማሻሻል ጉዳይ ላይ ብቻ ነበር፡፡
ፕሬዚዳንት ሞርሲ፣ራሳቸውን የህዝብ መሪ ከማድረግ ይልቅ በለየለት አምባገነንት ህዝባዊው አብዮት ያስወገዳቸውን ፕሬዚዳንት ሙባረክን ለመተካት አለመጠን መጣደፋቸውን የተገነዘበው የግብጽ ህዝብ፣ “ኧረ እርሶ ሰውዬ ያድቡ!” በማለት በየጊዜው ማሳሰቢያውን ቢሰጥም እርሳቸው ግን የሚሰሙበት ጆሮ አልነበራቸውም፡፡ ይልቁንስ “ሁሉም ነገር ወደ ብቸኛ የስልጣን ባለቤትነትና አምባገነንነት!” በማለት ሲጋልቡ ነገር አለሙን ሁሉ እርግፍ አድርገው ተውት፡፡ በርካታ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ቀስ በቀስ ስር እየሰደዱ በመምጣት፣ ግብጽንና ግብፃውያንን እግር ተወርች ጠፍረው አላላውስ አሏቸው፡፡
ቻይናውያን “አስፈሪው ማዕበል እንዳለፈ ሰላምና መረጋጋት ይሆናል” የሚል አባባል አላቸው፡፡ ግብፃውያንም የህይወትና የአካል መስዋዕትነት የከፈሉበት ህዝባዊው የአብዮት ማዕበል እንዳለፈ ሰላማዊ፣ የተረጋጋና፣ አዲስ ዲሞክራሲያዊ ህይወት ይከተለናል ብለው በእጅጉ ተስፋ አድርገው ነበር፡፡ በሀገራቸው ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ባካሄዱት ህዝባዊ ምርጫ አማካኝነት የመሪነቱን ስልጣን ከታላቅ አደራና ማሳሰቢያ ጋር ለሞሃመድ ሞርሲ የሰጡትም ወደ አዲሱ ህይወት ይወስዱናል በሚል ተስፋ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ አብዮታቸውን በመቀልበስ ይህን ታላቅ ተስፋቸውን አዲሱ ፕሬዚዳንት ሞሀመድ ሞርሲ በጥቂት ወራት እድሜ ብቻ እንደጉም እንዳበነኑባቸው የተረዱት ወዲያውኑ ነበር፡፡ ግብፃውያን በተደጋጋሚ ቃል የገቡትን እንዲፈጽሙ ፕሬዚዳንት ሞርሲን ቢያሳስቡም በጄ ሊሏቸው አልቻሉም፡፡ እንዲህ ያለውን የፕሬዚዳንቱን እብለት እንደተረዱም በከፍተኛ ትዕግስት የሰጧቸውን የአንድ አመት ቀነ ገደብ እያንዳንዱን ቀን በመቁጠር ማስላት ጀመሩ፡፡
ጋናውያን “በተደጋጋሚ ሙከራ ጦጣ ከዛፍ ወደ ዛፍ ላይ መዝለልን ትማራለች” የሚል አንድ አገርኛ አባባል አዘውትረው ይናገራሉ፡፡ ግብፃውያንም ያልፈለጉትን የአገዛዝ ስርአት በህዝባዊ አመጽ ማስወገድ እንደሚችሉ በተደጋጋሚ ጊዜ ወደ ዝነኛው የታህሪር አደባባይ ለተቃውሞ በመውጣት ማረጋገጥ ችለዋል፡፡ እናም ለፕሬዚዳንት ሞርሲ የሰጡት የአንድ አመት የጊዜ ገደብ እንደተጠናቀቀ፣ፕሬዚዳንት ሞርሲን ከስልጣናቸው ለመንቀል ዳግመኛ በሚሊየኖች ተጠራርተው፣ታህሪር አደባባይን በተቃውሞ አጨናነቁት፡፡ “ሞሐመድ ሞርሲ ጨዋታው አብቅቷል፣ በቃህ ውረድልን” ወዘተ የሚሉ መፈክሮችን አንግበው ፕሬዚዳንቱ አንጃ ግራንጃ ሳያበዙ፣ ስልጣናቸውን አስረክበው ወደሚሄዱበት እብስ እንዲሉ በግልጽ ቋንቋ ነገሯቸው፡፡ ፕሬዚዳንት ሞርሲ፣ የህዝቡን ድምጽ በጥሞና ለማዳመጥ በድጋሚ አሻፈረኝ አሉ፡፡ “ግብጽን ለአራት አመታት ለመምራት በዲሞክራሲያዊ አግባብ የተመረጥኩ ፕሬዚዳንት ስለሆንኩ፣የስልጣን ጊዜዬን ሳልጨርስ ከስልጣን አልወርድም በማለት አሻፈረኝ አሉ፡፡ ደጋፊዎቻቸውም ሀሳባቸውን በመደገፍ ከጐናቸው ተሰልፈው መቆማቸውን አረጋገጡ፡፡
የተቃዋሚዎቻቸው የተቃውሞ ማዕበል ግን ከደጋፊዎቻቸው በእጅጉ የላቀ ነበር፡፡ በመሀሉ ግን የሁለቱ ጐራ ግጭትና አተካሮ እየሰፋና እየከረረ፣ግብጽ ቀስ በቀስ ወደ አደገኛ ሁኔታ መንሸራተት ጀመረች፡፡ ድንገት ግን አንድ ያልተጠበቀ ክስተት ተፈጠረ፡፡ የግብጽ የጦር ሀይል ፕሬዚዳንቱን ከስልጣን በማስወገድ፣በቤት ውስጥ እስር እንዳዋለና በአንድ አቃቤ ህግ የሚመራ ጊዜያዊ መንግስት መቋቋሙን አሳወቀ፡፡ የፕሬዚዳንት ሙርሲ ተቃዋሚዎች በጦር ሀይሉ እርምጃ ጮቤ ሲረግጡ፣ ደጋፊዎቻቸው ደግሞ “ህገወጥ መፈንቅለ መንግስት ተደርጐባቸዋል” በሚል በተቃውሞ ካይሮን ቀውጢ አደረጓት፡፡ በዚህ ብቻ ሳይወሰኑም ሞሀመድ ሞርሲ ወደ ስልጣናቸው ካልተመለሱ ተቃውሞአቸውን መቼም ቢሆን እንደማያቆሙ በቁርጠኝነት አስታወቁ፡፡
አዲሱ ጊዜያዊ መንግስትና የጦር ሀይሉ ግን እስከ ባለፈው ማክሰኞ ድረስ የሞርሲን ደጋፊዎች በለዘብታ ሲያባብላቸው ቆየ፡፡ ማክሰኞ ግን ትእግስቱ ማለቁን በማሳወቅ ተቃዋሚዎች የታህሪር አደባባይን እንዲለቁ አለበለዚያ ጠበቅ ያለ እርምጃ እንደሚወስድ አሳሰበ፡፡ የፕሬዚዳንት ሞርሲ ደጋፊዎች ግን ለጦር ኃይሉ ማሳሰቢያ ቁብ አልሰጡትም፡፡ በዚህም ሳቢያ እስካሁን ድረስ በግብፅ ምድር ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ካይሮ በደም አላባ እንድትታጠብ ምክንያት ሆነ፡፡ እስከትናንት ድረስ ብቻ መንግስት በወሰደው የኃይል እርምጃ ሳቢያ 525 ግብፃውያን ህይወታቸውን አጡ፡፡ አሁን ሁሉንም የሚያስጨንቅ አንድ ጥያቄ - “የግብፅ የነገ እጣፈንታ ምን ይሆን?” የሚል ነው፡፡ ፈጣሪ ሰላሙን ያውርድላቸው!

Published in ከአለም ዙሪያ

ለአዲስ አበባ-ጅቡቲ የባቡር መስመር የ41 ባቡሮች ግዢ ኮንትራት ተፈርሟል
የኢትዮጵያ መንግስት ከያዛቸው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዶች መካከል በመላ ሃገሪቱ የባቡር መስመር ዝርጋታ ማከናወን አንዱ ነው፡፡ በአምስት አመቱ እቅድ ውስጥ በመላ ሃገሪቱ በ8 መስመሮች በጠቅላላ ይዘረጋል ተብሎ ከታሠበው 4744 ኪሎ ሜትር መስመር ውስጥ ከ2000 ኪሎ ሜትር በላይ ዘርግቶ ማጠናቀቅ እንደሚገባም ተመልክቷል፡፡ ከዚህ አንፃር ለማከናወን ከታሠበው እቅድ ውስጥ በተጨባጭ ወደ ተግባራዊ ስራ ተገብቶ ያለው የአዲስ አበባ (ሠበታ) - ጅቡቲ የባቡር መስመር ዝርጋታ ነው፡፡ ሌሎቹም በየደረጃቸው በተለያዩ የቅድመ ግንባታ ሂደት ላይ መሆናቸውን ይህን እቅድ እንዲያስፋፉም በ2000 ዓ.ም የተቋቋመው የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ይገልፃል፡፡ 

ለመሆኑ ፕሮጀክቱ ምን ላይ ደረሠ? እንዴስት እየተከናወነ ነው? ከተጠናቀቀ በኋላስ የሚኖረው ገፅታ ምን ይመስላል? በሚሉት ጉዳዮች ዙርያ ለኮርፖሬሽኑ የኮንትራት አስተዳደር ሃላፊ እና የአዲስ አበባ /ሠበታ/ ጅቡቲ ቺፍ ፕሮጀክት ማናጀር ለሆኑት ኢ/ር ካሣ ታረቀኝ ጥያቄዎችን አቅርበንላቸው የሠጡትን ምላሽ በሚከተለው መልኩ አጠናቅረነዋል፡፡

አጠቃላይ ስለ ፕሮጀክቱ
ፕሮጀክቱ በሁለት ክፍሎች የተከፋፈለ ሲሆን በመጀመሪያ ምዕራፍ እና በሁለተኛ ምዕራፍ በ8 የሃገሪቱ አቅጣጫዎች ወይም መስመሮች ግንባታው ይከናወናል፡፡ በስምንቱ መስመሮች በጠቅላላው 4744 ኪሎ ሜትር አካባቢ የሚሸፈን ሲሆን ከዚህ ውስጥ በመጀመሪያው ምዕራፍ 2397 ኪሎ ሜትር ያህሉን ሠርቶ ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዟል፡፡ ስምንቱ መስመሮች፡-
656 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የአዲስ አበባ-ሞጆ-አዋሽ-ድሬዳዋ- ደወሌ ወደ ጅቡቲ የሚሄደው
905 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ሞጆ-ሻሸመኔ/ሃዋሳ/-ኮንሶ-ወይጦ-ሞያሌ ወደ ኬንያ የሚሄደው
740 እና 115 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው - ከአዲስ አበባ - ኢጃጅ-ጅማ-ጉራፈረዳ-ዲማ-በደሌ ደርሶ ቀጥታ ወደ ደቡብ ሱዳን የሚራዘም
460 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው ኢጃጂ-ነቀምት-አሶሣ-ኩምሩክ የሚደርሠው
757 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የአዋሽ-ኮምቦልቻ-መቀሌ-ሽሬ መስመር
734 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የፍኖተ ሠላም-ባህር ዳር-ወረታ-ወልድያ ሠመራ-ኤልዳር መስመር
244 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የወረታ-አዘዞ-መተማ-ሱዳን መስመር
248 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የአዳማ-ኢንደቶ-ጋሠራ መስመር ናቸው፡፡
ከነዚህ ፕሮጀክቶች መካከል በቀጥታ ወደ ግንባታ ተገብቶ እየተሠራ ያለው የአዲስ አበባ/ሠበታ/ - ጅቡቲ መስመር መሆኑን ኢ/ር ካሣ ይገልፃሉ፡፡ በአሁኑ ሠአት በግንባታ ላይ ያለው ይህ መስመር ለሁለት ተከፍሎ የሚሠራ ሲሆን ከሠበታ እስከ ሜኤሶ ያለውን 317 ኪሎ ሜትር የቻይናው CREC የተባለ ኩባንያ በ1.84 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ጨረታውን አሸንፎ እየሠራ ይገኛል፡፡ በአጠቃላይ ከተያዘለት እቅድም እስካሁን 22 በመቶ የሚሆነው የተከናወነ ሲሆን በ2005 ይሠራል ተብሎ ከታሠበው ደግሞ 95 በመቶው ተሠርቷል፡፡ ከሜኤሶ-ደዋን ሌ/ጅቡቲ የሚዘረጋውን የፕሮጀክቱ ሁለተኛ ክፍል በአጠቃላይ 339 ኪሎ ሜትር የሚደርስ ሲሆን ግንባታው በቻይናው CCECC ኩባንያ ይከናወናል፡፡ የተያዘለት በጀትም 1.4 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ሲሆን በአጠቃላይ እስካሁን 20 በመቶ ተከናውኗል፡፡ በ2005 ከተያዘው እቅድ ውስጥ ደግሞ 70 በመቶው ተሠርቷል፡፡
ፕሮጀክቱን በታቀደለት ጊዜ ለማከናወን የገንዘብ ችግር ማነቆ መሆኑን የሚገልፀው ኮርፖሬሽኑ፤ሌሎቹም ጥናታቸው ተጠናቆ ገንዘብ በማፈላለግ ላይ እንዲሁም ውል ተፈርሞ ወደ ግንባታ ለመግባት በመንደርደር ላይ መሆናቸውን ይጠቁማል፡፡
ጥናታቸው ተጠናቆ ገንዘብ በማፈላለግ ላይ ያሉት ፕሮጀክቶች ኮንትራታቸው ለሩስያ የተሠጠው የሞጆ-ሻሸመኔ-ወይጦ መስመር እና ለብራዚል የተሠጠው የአዲስ አበባ /ሠበታ/-ጅማ- በደሌ መስመር ናቸው፡፡ ውላቸው ተፈርሞ ወደ ግንባታ ሊገቡ ያሉት ደግሞ YAPI Merkezi በተባለ የቱርክ ስራ ተቋራጭ የሚገነባው የ389 ኪሎ ሜትር ሽፋን ያለው የአዋሽ-ወልዲያ /ሀራገያ/ መስመር፣ CCCC ለተባለ የቻይና ኩባንያ የተሠጠው 268 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የወልድያ መቀሌ መስመር እንዲሁም CRI8G እና CGGC በተባሉ የቻይና ስራ ተቋራጮች የሚገነባው 229 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የወልዲያ-አሣይታ መስመር ናቸው፡፡ በጨረታ ሂደት ላይ ያለው ደግሞ 210 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የአሣይታ-ታጁራ መስመር መሆኑን ኢ/ር ካሣ ገልፀዋል፡፡

ፕሮጀክቶቹ መቼ ይጠናቀቃሉ?
የአዲስ አበባ/ሠበታ/ - ሚኤሶ የተያዘለት የግንባታ ዘመን ሶስት አመት ከአምስት ወር ሲሆን እስከ ነሐሴ 2007 ይጠናቀቃል ተብሎ ይታሠባል፡፡ በተመሣሣይ ከሜኤሶ-ዳዋንሌ/ጅቡቲ/ ያለው መስመርም የሶስት አመት ከ5ወር ጊዜ የተያዘለት ሲሆን በጥቅምት 2007 ይጠናቀቃል ተብሎ ይታሠባል፡፡ ለሌሎቹ ፕሮጀክቶች የተቀመጠ የመጀመሪያና የመጨረሻ የጊዜ ገደብ የለም፡፡

ስለ ባቡሮች
በ2018 ይጠናቀቃል ተብሎ ለሚታሠበው የአ.አ/ሠበታ/-ጅቡቲ መስመር በጠቅላላው 41 ባቡሮች እንዲሠማሩ እቅድ ተይዟል፡፡ ለባቡሮቹ ግዢም 259 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ተመድቧል፡፡ ባቡሮቹ በአብዛኛው ከቻይና የሚመጡ ሲሆን የግዥ ኮንትራታቸውም ከወዲሁ ተፈርሟል፣የመከላከያ ኢንጅነሪንግ የተወሰኑትን የፉርጐ ግንባታዎችን እንደሚያከናውን ተመልክቷል፡፡
ባቡሮቹ ሁለት አይነት ሲሆኑ በኤሌክትሪክ የሚሠራው HXDIC/7200 ኪሎ ዋት ሲሆን በነዳጅ የሚሠሩት DF7G/2200 ኪሎ ዋት ይባላሉ፡፡ ቴክኖሎጂያቸውም ባለ 1435 ስታንዳርድ ስምንት እጅ የአውሮፓ እና የቻይና ተዳቃይ ነው፡፡ በመጀመሪያው ዙር ከሚገቡት 41 ባቡሮች 35 ያህሉ የኤሌክትሪክ ሲሆኑ 6 የነዳጅ ባቡሮች ይኖራሉ፡፡ በነዳጅ የሚሠሩት አገልግሎታቸው ወደብ አካባቢ ላይ ያሉ እቃዎችን ወደ ዋናው መስመር ማጓጓዝ ይሆናል፡፡ የትራንስፖርቱን አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ የሚሠጡት የኤሌክትሪኮቹ ናቸው፡፡ ከ35ቱ የኤሌክትሪክ ባቡሮች ከ3-5 የሚደርሡት ለሠው ትራንስፖርት ሲውሉ ቀሪዎቹ እቃ ማጓጓዝ ተቀዳሚ ስራቸው ይሆናል፡፡ አርባ አንዱ ባቡሮች በአጠቃላይ 1130 ተጐታቾች (ፉርጐዎች) ይኖራቸዋል፡፡ ሠው የማጓጓዝ አቅማቸውን ስንመለከት አንድ ሎኮምቲቭ 10 ኮችዎች (ፉርጐዎች) እንዲጐትት ይደረጋል፡፡ አንዱ ኮች በአንደኛ ማዕረግ 56 ሰዎችን፣ በሁለተኛ ማዕረግ 80 ሰዎችን ይይዛል፡፡ አስሩ በጠቅላላው 560 እና 800 ሰዎችን ይይዛሉ፡፡
የእቃ ባቡሮቹ ስንመለከት 30 ዋገኖችን (ፉርጐዎች) እንዲጐትት የሚደረግ ሲሆን ከ3500-4000 ቶን እቃ እንዲጭን ይደረጋል፡፡
የባቡሮቹን ፍጥነት ስንመለከት፣ ለሠው የሚመደቡት በሠአት 120 ኪሎ ሜትር ሲፈጥኑ፣ ለእቃ የሚመደቡት 80 ኪሎ ሜትር በሠአት ፍጥነት ይኖራቸዋል፡፡ የምልልስ ብዛታቸው አገልግሎቱ ሲጀመር ፍላጐትን መሠረት አድርጐ የሚወሠን ይሆናል፡፡
ባቡሮቹ ሙሉ ለሙሉ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ እንደመሆናቸው ድንገት ኤሌክትሪክ ቢቋረጥ ምን ይሆናሉ ለሚለው ስጋት ሁሌም እስከ ቀጣይ ጣቢያ ሊያደርስ የሚችል በቂ የሆነ በትርፍነት የሚጠራቀም ሃይል ይኖራቸዋል ብለዋል ኢ/ር ካሣ፡፡ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት ላይም በተመሣሣይ እንዲህ አይነት ቴክኖሎጂን የሚጠቀሙ ባቡሮች ወደ ስራ እንደሚገቡ ተገልጿል፡፡

ባቡር ነጂዎችን በተመለከተ
እስካሁን ሠልጣኞች የሚመረጡበት መስፈርት የተዘጋጀ ሲሆን ከባቡሮቹ ግዢ ጋር በኮንትራቱ ተካቶ በእቅድ ተይዟል፡፡ በቀጣይ ባለሙያዎች በተዘጋጁት መስፈርቶች መሠረት ተመልምለው እንዲሠለጥኑ ይደረጋል፡፡

Published in ባህል
Saturday, 17 August 2013 11:48

ግራኝ ሆኖ የመፈጠር ጣጣ!

አንዳንዴ ለነገሮች የምንሰጠው ትርጓሜ እንደየአካባቢያችን ዓውድ ይወስናል፡፡ በዚህ ዐውድ ውስጥ ደግሞ ባህል፣ ልማድና እምነት የየራሳቸውን ፈንታ ያዋጣሉ፡፡ በተፈጥሮ የተቀበልናቸውን ነገሮች ማህበረሰብ፣ ቤተሰብና አካባቢ እንደልምዳቸውና ዝንባሌያቸው ሞገስ ሊሰጡን፣ ወይም ዝቅ አድርገው ሊፈርጁን የሚችሉበት ቀጥተኛ ያልሆነ ሥልጣን አላቸው፡፡
እኔም ዛሬ ከዓለማችን ፀሐፍት አንደበት ተውሼ፣ አብሬያቸው ተካፍዬ የማስነብበው ርዕሰ ጉዳዩ የዚሁ መነሻ ውጤት ነው፡፡ በተፈጥሮ “ግራኝ” ተብለው ስለሚጠሩት፣ ከቀኝ እጃቸው ይልቅ የግራ እጃቸው ለክፉና ለደግ ስለሚፈጥነው ሰዎች ሕብረተሰቡ ምን ይላል? ዓለማችን ግራኞችን በግራ ዓይን ለምን ማየት አሰኛት? የሚለውን ጥያቄ አንስተው መልሱን ከታሪክ የተቀበሉ ምሁራንን በሮች እያንኳኳሁ ጥቂት ለማለት ፈልጌያለሁ፡፡
ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ጊዜ ሰጥተው፣ ቀልባቸውን ሰብስበው ያጠኑ ምሁራን እንደሚሉት ከሆነ፤ ብዛታቸው በቁጥር (በፐርሰንት) ሲሰላ ከአጠቃላይ የዓለማችን ሕዝብ ቁጥር 10% ያህሉን ይይዛሉ፡፡ ታዲያ እነዚህ በቁጥር ስሌት ከቀኝ እጅ ተጠቃሚዎቹ በቁጥር የሚያንሱ ሰዎች በአብዛኛው በጥሩ ዓይን አይታዩም፤ እንዳልታደለ፣ ወይም ዕድል እንዳልቀናው ይታሰባሉ፡፡ ግራኞች እንደ ግራ መጋባት ይቆጠራሉ፡፡ ይህ አተያይ ደግሞ በእኛ በአፍሪካዊያን ላይ የበለጠ ጫና ይፈጥራል፡፡ ይሁን እንጂ ታሪክ እንደሚያሳየን ታላቁ ቀራፂ ሚካኤል አንጀሎ፣ ጁሊየስ ቄሣር፣ ሌዮናርዶ ዳቪንቺ፣ ቢልክሊንተንናም ባራክ ኦባማ ግራኝ ከሚባሉት ናቸው፡፡
በርግጥም እንደታሪክ ፀሐፍቱ መረጃና አባባል ከሆነ፤ ግራኝ የሆኑ ሰዎች ከእኛ በምንም ነገር አይተናነሱም፡፡ በአእምሮ ብቃት መለኪያም ሆነ በተግባር አንዳች ጉድለት የለባቸውም፡፡ ግን በተለያየ አምልኳዊና ጥንታዊ ልማዶች መነሻነት፤ በሃይማኖታዊ መጽሐፍት ውርስ ግራኝ መሆን ግራ ነው፡፡ ስለዚህም በቀኝ እጅ መጠቀም መልካም ዕጣ፣ ግራኝ መሆን ደግሞ ጣጣ ነው ተብሎ ሺህ ዓመታት ሲታሰብ ኖሯል፡፡
ዛሬም ያ ልክፍት እንደየሕብረተሰቡ የአስተሳሰብ ልቀትና ደረጃ ከፍና ዝቅ ባለ ሁኔታ ይታመናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ፍየሎች በግራ /ተኮናኞች/ሲል፣ በጐች/በቀኝ ፃድቃን ብሎ ስለሚያስቀምጥ፣ በሰይጣን ወገን የሚቆመውን የግራ ዕጣ መልካም ብሎ መቀበል ይከብዳል፡፡ ግን ግራኝ በራሱ ምን ግራ አለበት የሚለውን ጠልቆ ለማሰብ ጊዜና ቦታ ያለው ሰው ብዙ አይደለም፡፡ ስለዚህም ወላጆች ሕፃናት ልጆቻቸው ግራኝ እንዳይሆኑባቸው በማለት በግራ እጃቸው ሲበሉ፣ ወይም ሲሰሩ መከልከልና መቆጣት አለፍ ሲልም እስከዱላ ይደርሳሉ፡፡
ዞግቦ፣ የሚባሉ ፀሐፊና ተመራማሪ እንደሚሉት፤ በምንኖርባት ዓለም ግራኝ መሆን ከወንጀለኝነት አመፀኝነትና ከጥንቆላ ጋር ሳይቀር ይዛመዳል፡፡ ነገር ግን ግራኞች ከሌሎቻችን የተለየ የወንጀልና የዓመጽ ድርጊት ስለመፈፀማቸው የሚጠቁም አንዳች ጥናታዊ ማስረጃ የለም፡፡ ይልቅስ በሁሉም ነገራቸው እኛን መሰል ናቸው፡፡
አውሮፓውያኑ፣ በአጠቃላይ ምዕራባዊያኑ “You are right!” በማለት ቀኝን የትክክለኝነት ማሳያ አድርገው እንደተቀበሉ ሁሉ፤ እንዲያውም ከዚያ እጅግ ባለፈ ሁኔታ አፍሪካዊያኑ በቀኝ እጅ ያመልካሉ፡፡ ለቀኝ ይገዛሉ፡፡
በአፍሪካ ውስጥ ከምዕራብ አፍሪካ እስከመካከለኛው አፍሪካ፣ ግራኝ መሆን እንደ ክፉ ዕጣ የሚታይ ፍርጃ ነው፡፡ ከዳካር አንስቶ እስከ ኪንሻሳ በግራ እጅ መብላት፣ በግራ እጅ የቱንም እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ወይም ለተግባቦት መጠቀም በእጅጉ የተወገዘችና ለሌሎች ሰዎች አክብሮት እንደመንፈግ የሚቆጠር ድርጊት ነው፤ ከዚያም በላይ እንደስድብ ይቆጠራል፡፡
ለምሳሌ ኒጀር ውስጥ በሰሜናዊ ሣንጋይና ሃውስ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች በግራ እጃቸው በፍፁም ሰላምታ አይለዋወጡም፡፡ ምናልባት በቀኝ እጃቸው አንዳች ዕቃ ጨብጠው ቢሆን፣ ወይም በሌላ ጉዳይ መጠቀም ባይችሉ ቀኝ ክንዳቸውን ለሠላምታ ይዘረጋሉ እንጂ በግራ እጃቸው ሰላም ማለትን አይሞክሩትም፡፡ በግራ እጅ ሠላምታ ቀኑን ሸቃባ እንደማድረግ ይቆጠራል፡፡ ኮትዲቯር ውስጥ ቤቴ በሚባል አካባቢ ሴት ልጅ በግራ እጅዋ ምግብ ካበሰለች ነገር ተበላሸ፣ አገር ጠፋ! አሻፈረኝ ብላ ምናልባት እንኳ ብታበስል እንትን የነካው እንጨት ነው ምግቡ፡፡ እዚሁ ሥፍራ ካህን ይሁን ቄስ አሊያም መጋቢ የግራ እጁን አንስቶ ቃሉን ቢያስተምር ወይም ቢሰብክ ምዕመኑ ጉባኤውን እየተወ ሹልክ ብሎ ይወጣል፡፡ ምክንያቱም በግራ እጅ እርግማን እንጂ ባርኮት አይሰጥም፡፡ ታዲያ ማን ሞኝ አለ ከካህኑ እጅ እርግማንን የሚቀበል፡፡
በዚህችው ኮትዲቯር ውስጥ ዲያስ በምትባል ሥፍራ አንድ ሰው የሌላውን ሰው የትውልድ መንደር በግራ እጁ ጣት ከጠቆመ ነገር ተበላሸ ማለት ነው፡፡ ትርጓሜውም ያ በግራ እጅ የሚያመለክት ሰው እዚያ ለሚያሳየው መንደር ተወላጅ ያለው ከበሬታ ዝቅ ያለ ነው የሚል ነው፡፡
በቶጐም ተመሳሳይ ወይም ተቀራራቢነት ያለው የግራ ትርጔሜ አለ፡፡ ቶጐ/ጋንጋም/ ውስጥ አንድ ልጅ በግራ እግር ለምታት መሞከር የንቀት ንቀት ነው፡፡ ስለ ግራኞች ትንሽ ለየት ያለ ትርጓሜ የሚሰጠው ካሜሩን ውስጥ ግባያ የሚባል አካባቢ ነው፡፡ እዚያ ሀገር ላይ “ግራኝ አይስትም” የሚል ከአነጣጣሪነት ወይም ከጦረኝነት ጋር የሚዛመድ ትርጓሜ ይሰጣል፡፡
ቤኒን ውስጥ ባታናም በሚባል አካባቢም ከዚሁ ጋር ተመሳሳይ ሃሳብ ያለው እምነት አለ፡፡ ግራኞች ጀግና፣ አዋቂ፣ ተዐምረኛም ተደርገው ይታሰባሉ፡፡ ስለዚህም ሕዝቡ ባንድ ወገን ያከብራቸዋል፤ በሌላ ወገን ደግሞ ይፈራቸዋል፡፡ ምክንያቱም የተለየ ገድል እንደሚፈጽሙ ስለሚያስብ በጥንቃቄ ያያቸዋል፡፡
ይሁንና በዚህ ምድር ግራኝ ሰው ለሥልጣንና ለንግሥና ፈጽሞ አይታሰብም፡፡ የጦረኝነት መንፈስ አለበት ተብሎ ስለሚታሰብ የሕዝቡ ልብ አይተማመንባቸውም፡፡ እንደ ዓይነ ስውር፤ አካል ጉዳተኛ የሚታዩበትም አጋጣሚ አለ፡፡
በአፍሪካዊቷ ቡርኪናፋሶም ከዚሁ ጋር ተመሳሳይ ሆኖ ጀግንነታቸውን ከጦር ሜዳ ወደ አልጋ ይወስደዋል፡፡ ጉርማንቼ በምትባል አካባቢ ግራኝ፤ ከሚስቱ ጋር ፍቅርን ሲጋራ የተሳካለት ነው ተብሎ ይታመናል፡፡
ምክንያቱም በአልጋ ፍቅር ዋነኛው ተዋናይ ግራ እጅ ነው ተብሎ ስለሚገመት ነው፡፡ በዚህም የተነሳ እስካሁን ዘመን ድረስ ወንዶች ሲሞቱ መቃብራቸው ጉድጓድ ውስጥ የሚጋደሙት በግራ በኩል ወደ ምስራቅ ዞረው ነው፤ እዚያም ፍቅር መሥራት ይኖራል ብለው ስለሚያስቡ፡፡
ኮትዲቯር ውስጥ ኒያራፎሎ ደግሞ ወንዶች ሲቀበሩ በግራ ነው፤ ይህ የሚደረገው የቀኝ እጃቸው ባርኮት ለመስጠት ነፃ እንዲሆን ነው፡፡ ይህ ማለት ቀኝ ለባርኮት፣ ግራ ለእርግማን እንደማለት ነው፡፡
ሰሜን ቶጐ ጋንጋም ውስጥ ማንም ሰው በመኖሪያ ቤቱ ግራ ማዕዘን ላይ አይቀመጥም፤ ያ ግራ ሥፍራ ለሟች መቀበሪያ ነው፤ ትርጉሙም ግራ ከሞት ጋር የሚያጣምር ነው፡፡ እዚያ አካባቢ ክፉ ሞት ሞቷል የሚባልን ሰው በቀኝ እጁም ሆነ በቀኝ እግሩ እንዲህች ብሎ የሚነካው የለም፡፡ መቃብር ቆፋሪዎች በግራ እግራቸው ነው የሚነኩት፡፡
ግራ እጅ መንፈሳዊ መስዋዕት ለማድረግም አይመረጥም፤ ለሹመትም ሲሆን በቀኝ እጅ ተሿሚው ጭንቅላት ላይ እጅ ተጭኖ ወይም በቀኝ እጅ ወደ እርሱ እያመለከቱ ባርኮትና ሹመት ይሰጣል እንጂ በግራ አይሞከርም፡፡ የግራና ቀኝ ጉዳይ በቋንቋና ሥነ ልሳንም ውስጥ የተሳሳተተ ትርጓሜ ይሰጠዋል፡፡ ይሁንና በአብዛኛው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሚታየው የግራና የቀኝ ትርጓሜ በተለይም የብሉይ ኪዳን አዋቂዎች እንደሚሉት፤ አመጣጡ በጥንት ዘመን ዕብራዊያን ከጐረቤቶቻቸው የወረሱት ነው፡፡ በተለይ ከትንሿ እስያ፡፡ የቀኝን ሞገስ ማግኘትና ጥንካሬን በተመለከተ ከላይ የጠቀስኳቸው ፀሐፊ ያስቀመጡት መረጃ እንደሚያሳየው፤ ለምሳሌ ኢራቅ ውስጥ ከኖራ ድንጋይ የተሰራው ሃውልት የአምር ቀኝ እጅ ወደሌላው ንጉሥ ተዘርግቶ ይታያል፤ ይህ ቀኝ እጅ ስምምነትን ያሳያል፡፡ በሌላ ቦታ የግብፁ ፈርኦን (ከ1345-1318) ከክ/ል/በፊት ሆረስ ከሚባለው አምላክ ቀኝ ተቀምጦ ይታያል፡፡ ይህ ክብር ነው፡፡ በነዚህ ምሣሌዎች/መታሰቢያ ሃውልቶች/ ትርጓሜ ቀኝ ስምምነት፣ ስኬትና ባለአለኝታ መሆን ናቸው፡፡
እነዚህ ደግሞ በዕብራዊያን ታሪክ ገቡ፤ ከዚያም አደጉ፡፡ ተዘሩ፡፡ ኖሩና እንደ እንጀራ ክብ እየሰሩ ቀጥለዋል፡፡ ተደጋግመዋል፡፡ በማለት ጠቢባኑ አትተውልናል፡፡ ምሥጋና ይግባቸው!

Published in ህብረተሰብ

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…“እኔ ብቻ አዋቂ…” “እኔ ብቻ ልዩ…” “እኔ ብቻ…” ምናምን የሚሉ ነገሮች አልበዙባችሁም! አለ አይደል…በምንም ነገር እኛ ልዩ ሆነን ላይኛው ፎቅ ላይ የተቀመጥንና የተቀረው ሰው ሁሉ ደግሞ ‘ምድር ቤት’ ያለ የምናስመስል እየበዛን ነው፡፡
አንዳንዴ ስታስቡት…“ብሶትና ችግር አውርተን እስከመቼ…” ትላላችሁ፡ ብሶቱና ችግሩ እየበዛ ነዋ! ሁሉ ነገራችን… አለ አይደል… ትንሽ ካፊያ የሚያጥበው የእንትናዬዎቻችንን ‘ኩልና ፋውንዴሽን’ እየሆነ ነው፡፡ ማስመሰል፣ መመሳሰል… አንዲት ስንጥር ሳናነሳ “ዱታው ዘራፍ…” “ግነን በሉኝ…” አይነት ነገሮች ‘ተቀባይነት ያላቸው’ ነገሮች እየሆኑ ነው፡፡
ስሙኝማ…እስቲ ‘ቦተሊካችንን’ ነገሬ ብላችሁ ስሙት…ሁሉም ወገን…አለ አይደል…“ዱታው ዘራፍ…” “ግነን በሉኝ…” ሲል ነው የምትሰሙት፡ አንዳንዴ ምን ይገርመኛል መሰላቸሁ…ሁሉም ወገኖች የሚጠቀሙበት ቋንቋ ተመሳሳይ ከመሆኑ የተነሳ…ይቺን ነገር ማታ ውስኪ ላይ ተመካክረው ነው እንዴ ጠዋት ለእኛ የሚበትኑት ምናምን እንላለን፡፡ አሀ… “ሊበራል ዲሞክራት ነኝ…” የሚለውም፣ “ኒኦ ሊበራል ነህ…” የሚባለውም ልዩነቱ ነጠላ ሰረዝ ላይ ብቻ የሆነ ነገር ሲናገሩ የማንጠረጥርሳ!
እናላችሁ…አንዳንዴ ስታስቡት በ“እኔ ብቻ ትክክል…” የተቃኘው የዚህ አገር ‘ቦተሊካና ቦተሊከኞቹ’ ነገር ግራ አይገባችሁም! አዲስ ሀሳብ ናፈቀን! አሀ…ልክ ነዋ! ዘላለም ‘ሊበራል ቅብጥርስዮ’ ‘ምናምን ሰብሳቢ’ እየሰማን መኖር ሰለቸና! ኮሚኩ ነገር ምን መሰላችሁ…አንዳንድ ‘ቦተሊከኞች’…አለ አይደል…ልክ የማርክስን ‘በትረ መንግሥት’ እንደተቀበሉ ነገር ሲያደርጋቸው ስታዩ…በቃ የ‘ቲራቲር’ አገር ሆነን ቀረን ያስብላችኋል፡፡
ስሙኝማ…‘ቦሶቻችን’ ለምን ኮስተር እንደሚሉ ገርሟችሁ አያውቅም! ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…በቃ ወንበር ስንይዝ…አለ አይደል…ያቺ የ‘ባላባትነት ሜንታሊቲ’ በእግረ ሙቅ የምትጠፍረን ይመስለኛል። አለ አይደል… ወንበር መያዝን ከሥራ ሀላፊነት ይልቅ በሰው ልጅ ላይ ‘ውሀ እየረጩ’ ለመሄድ የተሰጠ ‘ሊቼንሳ’ ምናምን ነገር እናደርገዋለን፡፡
እናማ…“ውሀ ረጨኸኝ እኮ!” ብትሉ…አለ አይደል… “እና ብትረጭስ ምን ታመጣለህ…” አይነት የ‘ፎቅ ቤትና የምድር ቤት’ ነገር እየበዛ ነው፡፡ እንዴት እንደሆነ እንጃ እንጂ…በ‘ፎቅ ቤትና የምድር ቤት’ አስተሳሰብ…‘የተለየን’ የመሆን ስሜት የሚያሳድርብን ሰዎች ቁጥራችን በድምር ሳይሆን በብዜት እየጨመረ ነው፡፡ ጥያቄ አለን አንዳንድ ሰዎች የታርጋቸው መለያ ኮድ ብቻ የትራፊክን ህግ እንደፈለጉ እንዲጥሱ የሚያደርጋቸው …አለ አይደል…በታርጋዋ ብቻ የ‘ፎቅ ቤትና የምድር ቤት’ አስተሳሰብ ስለሚያድርባቸው አይመስላችሁም!
ታዲያላችሁ… ይቺ የ‘ፎቅ ቤትና የምድር ቤት’ አስተሳሰብ በተለይ በስነ ጥበቡ አካባቢ ግንኙነቶችን እያበላሸ ነው፡፡ አሥር ሰው ባጨበጨበ ‘ኤጓቸው’ በአሥር እጥፍ እየናረ ባልሆነ አቅጣጫ ‘የሚታጠፉ’ ሰዎች እያየን ነው፡፡
እናማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…‘ሴሌብሪቲዎቻችን’ ስሙኝማ…ምን የምትል ነገር አለች መሰላችሁ…“ገንፎ እፍ እፍ ቢሉሽ ሊውጡሽ ነው፤ እውነት አይምሰልሽ፣” የሚሏት ነገር አለች፡፡ እናማ… ጭብጨባ ሁሉ የእርፍና መለኪያ እንዳልሆነ ልብ በሉልንማ! አሀ ልክ ነዋ…አብዛኞቹ ነገሮች በ‘ቲፎዞ’ ብዛት እየተሠሩ ባሉበት ዘመን…ከልብ ያልሆነ የይሉኝታ ጭብጨባ ብዙ ልጆችን እያሳሳታቸው ነው፡፡ (እግረ መንገዴን…አብዛኛው በየአዳራሹ የምናሰማው ጭብጨባ የ‘ይሉኝታ’ እንጂ ‘ቦሱ’…አለ አይደል… “ትምህርት ለአንድ አገር እድገት አስፈላጊ…” መሆኑን ስለነገሩን በ‘አስተሳሰባቸው ምጥቀት’ ተመስጠን እንዳልሆነ ይጻፍልንማ! ቂ…ቂ…ቂ…)
እናላችሁ…ተዋናያኖቻችን ወይ በፊልም፣ ወይ በድራማ ትንሽ ሲታወቁ…የአራዶቹን ቋንቋ ለመጠቀም ‘መነስነስ’ ያበዛሉ ይባላል፡፡ እንዲህ ነዋ የሚባለው! ታዲያላችሁ…የ‘ፎቅ ቤትና የምድር ቤት’ አስተሳሰብ ውስጥ ይገቡና ለሥራ የሚጠይቁትም ዋጋ የመለስተኛ ድርጅት ዓመታዊ ገቢ ወደመሆኑ እየተቃረበ ነው አሉ፡፡
ነገርየው… አለ አይደል…
“አይታ የማታውቀውን የሰው ጃኖ ለብሳ፣
ተመለሺ ቢሏት መቼ ተመልሳ…”
አይነት እየሆነላችሁ ነው፡፡ ትንሽ ማበረታቻ እንደ ‘ፍጹምነት’ ማረጋገጫ እየታየ…አለ አይደል… “የት ይደርሳሉ…” የተባሉ ሰዎች ባቡራቸው መሀል ላይ እየተሰናከለ ነው፡፡
ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ኳስ ተጫዋቾቻችን ‘ተዘዋወሩባቸው የሚባለውን የገንዘብ መጠን እየሰማን…“ጉድ!” እያልን እንደሆነ ይመዝገብልንማ፡፡ ብቻ…ያንን ያህል ገንዘብ የሚያወጡ ክለቦች የየራሳቸውን ሜዳ መቼ ሊሠሩ እንዳሰቡ ይንገሩንማ… ‘ለመሥራት ካሰቡ’ ማለታችን ነው፡፡ በነገራችን ላይ…አንዳንዴ “በኳስ ክለቦቹ መሀል የ‘ፎቅ ቤትና የምድር ቤት’ አስተሳሰብ አለ እንዴ!” የምንል መአት ነን፡፡ ልክ ነዋ…ከክለቦች ጀርባ ገንዘብ… ከገንዘብ ጀርባ ሰዎች… ከሰዎች ጀርባ ‘ኤጎ’…ምናምን እያለ የሚቀጥል ነገር ሊኖር ይችላል ብሎ መጠርጠር ክፋት የለውማ!”)
እናላችሁ…የ‘ፎቅ ቤትና የምድር ቤት’ አስተሳሰብ ለብዙ ነገሮች መሰናክል ምክንያት እየሆኑ ነው፡፡ ጓደኝነቶች፣ ወዳጅነቶች፣ ውህደቶች…ምናምን ሁሉ ‘እንዳማረባቸው የማይዘልቁት’…በመሀል የ‘ፎቅ ቤትና የምድር ቤት’ አስተሳሰብ ዘልቆ ስለሚገባ አይመስላችሁም!
እናላችሁ…‘ምግብ በአዲስ መልክ ጀምረናል’ ይባልና ስትገቡ አርባ ምናምን የምግብ አይነት ከፍተኛ ‘ሽብር’ በተካሄደበት ‘ስፔሊንግ’ የተጻፈበት የምግብ ዝርዝር ይቀረብላችኋል፡፡ ታዲያ ምን መሰላችሁ…ሠላሳ ዘጠኙ የምግብ አይነት አይኖርም። ግን ይቺ “ምግብ በአዲስ መልክ ጀምረናል…”፣ “እጅ የሚያስቆረጥም …እንሠራለን…” ነገሮች ከጀርባቸው “ከሌሎች የተሻልን ነን… አይነት የ‘ፎቅ ቤትና የምድር ቤት’ ነገር አለባቸው፡፡
ከመደበኛዋ ስምንት የሥራ ሰዓት ሦስቷን እንኳን በስነ ስርአት የማይሠሩ ድርጅቶች “የሃያ አራት ሰዓት አገልግሎት እንሰጣለን…” ሲሉ ብዙ ጊዜ ከጀርባ ያቺ ባህል ነገር የሆነችው የ‘ፎቅ ቤትና የምድር ቤት’ አስተሳሰብ አለች፡፡
ብዙ ማስታወቂያዎች ላይ የሚጠቀሙባቸውን ቃላት ነገሬ ካላችሁ…“ማን እንደ እኛ!” አይነት የ‘ፎቅ ቤትና የምድር ቤት’ አስተሳሰብ ያላቸው ናቸው፡፡
የእኔ ቢጤዎች ደግሞ አለንላችሁ…አንድ መጽሐፍ ስለተረጎምን፣ አንዲት የግጥም መጽሐፍ ስላስመረቅን የ‘ፎቅ ቤትና የምድር ቤት’ አስተሳሰብ እያደረብን “ምን ተርጓሚ አለና ነው…” “አሁን እዚህ አገር ገጣሚ አለ!...” የምንል፡፡
እግረ መንገድ…ይቺን ስሙኝማ…ይሄ የፌስቡክ ዘመን ጣጣ…ትንሽዬው ልጀ እናቱን “እማዬ ወደዚህ ዓለም የመጣሁት ‘ዳውንሎድ’ ተደርጌ ነው እንዴ?” ብሎ ይጠይቃታል.፡ እናቱ ምን ብላ መለሰችለት መሰላችሁ…“አይ ‘ዳውንሎድ’ ተደርገህ አይደለም፡ ተወልደህ ነው፡፡” አሪፍ ምሳሌ አይደል!
እናላችሁ… ነገሮች አሁኑኑ በብልጠት ካልተያዙ ነገና ተነገ ወዲያ…“እማዬ ወደዚህ ዓለም የመጣሁት ‘ዳውንሎድ’ ተደርጌ ነው እንዴ?” የሚሉ ልጆች የማይበዙበት ምክንያት የለም፡፡ ነገርዬው ምን መሰላችሁ… ዘንድሮ ብዙ ወላጆች በ‘ፎቅ ቤትና የምድር ቤት’ አስተሳሰብ ‘ከሌሎች ለመለየት’ ልጆቻቸውን ዕድሜያቸው ለማይመጥናቸው ነገሮች እያጋለጧቸው ነው፡፡ አንዳንዴ እኮ…እዚቹ ከተማችን ውስጥ ብቻ እየተፈጠሩ ያሉትን ነገሮች ስታስቡ ከአንድና ከሁለት አሥርት ዓመታት በኋላ ነገሮች ሊደርሱበት የሚችሉበት ደረጃ ያሳስባችኋል።
ቢ.ኤምደብልዩ ያለው እንትና ስለያዘች ብቻ የ‘ፎቅ ቤትና የምድር ቤት’ አይነት ነገር የሚጠፍራት መአት አለች፡፡ በአንድ ቡና በወተት አምስት ሰዓት ሙሉ ‘ወንበር ስታግል’ እንዳልዋለች ሁሉ ‘መኪና ላይ ስትወጣ’… “በእናታችሁ፣ ማኪያቶ፣ ቡና በወተት ምናምን አይሰለቻችሁም!” አይነት ‘ዘጠነኛው ደመና’ ላይ መንጠላጠል ትጀምራለች፡፡
እግረ መንገዴን…አንዱ ምን አለ ይባላል መሰላችሁ… “ሴቶች አስቸጋሪ ፍጡራን ናቸው፡፡ ዕድሜያቸውን ስትጠይቃቸው ኮረንቲ ሊጨብጡ ይደርሳሉ፡፡ የልደት ቀናቸውን ስትረሳ ግን ዘልዝለው ቢበሉህ ደስ ይላቸዋል፡፡” ደግነቱ ዘንድሮ ልደት ላይ “ለመሆኑ ዕድሜሽ ስንት ደረሰ?” እያሉ ቁጥር መጠያያቅ ‘ጎጂ ልማድ’ ስለሆነ… እየቀረልን ነው፡፡
ከዚህ በፊት ያወራናትን እንድገማትማ…ሰውየው ዕድሜውን ሲጠየቅ ወደ ሀያ ምናምኑን ይገነድስና “ሠላሳ…” ምናምን ይላል፡፡ ሌላኛው ደግሞ የእሱን ዕድሜ ሲጠየቅ ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው…“በእሱ ስሌት ከሆነ እኔ ገና አልተወለድኩም!” ቂ…ቂ…ቂ…በዛሬው ቀን በራሳቸው የዕድሜ ስሌት ‘ሳይወለዱ ልደታቸውን ለሚያከብሩ’ ሁሉ… መልካም ልደት ብለናል፡፡
እናላችሁ…የ‘ፎቅ ቤትና የምድር ቤት’ አስተሳሰብ…(እንደውም በቋፍ ነን!) ነገሮችን በ“አንተ ትብስ አንቺ…” እንዳንሠራ እያደረገን ነው እላችኋለሁ፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Published in ባህል

የፌዴሬሽን ነገር አልተሳካልንም!
ሩጫ እንደ አፍ አይቀናም (ለአትሌቲክስ ፌዴሬሽን!)

.የዛሬውን ፖለቲካዊ ወጌን የምጀምረው በአትሌቲክስ ነው፡፡ አትሌቲክስና ፖለቲካ ምን አገናኛቸው እንዳትሉኝ ብቻ! (ቀላል ይገናኛሉ!) ወዳጆቼ … አትሌቲክስ ስፖርትነቱ ለጀግኖች አትሌቶቻችን ነው እንጂ ወደ ኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሲገባ መልኩን ይቀይራል፡፡ (የቀለጠ ፖለቲካ ይሆናል!) ይሄ እኮ ሃሜት አይደለም፡፡ በመረጃም በማስረጃም የተደገፈ ሃቅ ነው (ፍ/ቤት የመሄድ ፍላጐት ግን የለኝም!) ለነገሩ ፍ/ቤትም ለካ እረፍት ላይ ነው፡፡ እናንተዬ … ፍ/ቤት በክረምት የሚዘጋው (የሚያርፈው) ድሮ ወንዝ እየሞላ መሻገሪያ ስለሚጠፋ ነው የሚባለው እውነት ነው እንዴ? አሁን ታዲያ የትኛው ወንዝ አስቸግሮን ይሆን? (የልማድ እስረኞች እኮ ነን!) 

ይሄውላችሁ … ስለ ፌዴሬሽኑ ፖለቲካ ከማውጋታችን በፊት ትንሽ “ሰለብሬት” ማድረግ አለብን - ስለ አትሌቶቻችን ድል!! እናንተ … የጦቢያ አትሌቶች እንዴት አንጀት አርስ ናቸው ባካችሁ! (ኧረ ሺ ጊዜ ይመቻቸው!) ለዓለማችን ኮከብ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ (እውነትም ነገር የገባት ሰጐን!) እጅ ነስቻለሁ! ለ800 ሜትር የወርቅ ሜዳልያ ባለድሉ ለመሃመድ አማንም እጅ ነስቼአለሁ - በአዲስ ርቀት ላስመዘገበው ድንቅ ውጤት! ነሐስን ጨምሮ ሌሎች ድሎችን (ከ4-10 ለወጡትም) ላገኙም እጅ ነስቼአለሁ፡፡ ለደረጃ ባይበቁም ጦቢያን አደባባይ ወክለው ለሮጡልን ምርጥ የአገሬ ልጆችም እጅ ነስቼአለሁ፡፡ በሴቶች ማራቶን በገጠማቸው አንዳንድ እክሎች ውድድሩን አቋርጠው ለወጡት የጦቢያ ጀግና አትሌቶችም እጅ ነስቼአለሁ (ፌዴሬሽኑ ደብዳቤ ፃፉ ቢልም) አንዳንዴ ምን እንደማስብ ታውቃላችሁ? ኢትዮጵያን የሚመሯት ምነው አትሌቶች በሆኑ እላለሁ (የድል አርማ ናቸዋ!)
እናላችሁ … በብዙ ጉዳዮች “ኮንሰንሰስ” ላይ የማይደርሰው የአበሻ ልጅ፣ በጥሩነሽ ድል እኩል ሲቦርቅ፣ እኩል ሲፈነድቅ፣ እኩል ሲቀኝ፣ እኩል ሲያደንቅና ሲያሞግስ አስተውዬ “ይሄ ህዝብ ጀግና ይወዳል” አልኩኝ (ጀግና ነው የጠፋው ማለት ነው?) እናላችሁ… ለወትሮው የፌዝ መድረክ የነበረው ፌስቡክ እንኳን አትሌቷን በማወዳደስ ሲባትል ነው የሰነበተላችሁ እውነትም ጀግና ይወዳል!
ኤፍሬም አማረ የተባለ ፀሐፊ ምን አለ መሰላችሁ? “የወርቅ እርግቢቷ ሞስኮም ላይ በረረች” (እሷ ማርስም ቢሆን ትበራለች!) እዚያው ፌስ ቡክ ላይ የሰፈረው ሌላው አስተያየት ደግሞ ኢትዮ ቴሌኮምን በሾርኒ ወጋ ያደርጋል - አትሌቷን እያደነቀ፡፡ እንዲህ ይላል፡-
“እቺ ጥሩዬ የሚሏት እንዴት ታድላለች
የኢትዮጵያን ኔትዎርክ በፍጥነት በልጣለች፡፡”
ግጥሟ ዘና ብታደርገኝም ንፅፅሩ ብዙም አልተዋጠልኝም፡፡ እንዴ… ሮኬትና ጋሪ እኮ ነው የተወዳደረው! አንድ የፌስቡክ ውዳሴ ደግሞ እነሆ (ለሰጐኒቷ!) “አሳፍራን የማታውቀው የወርቅ መአድኗ (አዶላ ማለት ይቻላል) ኢትዮጵያዊቷ ጥሩነሽ ዲባባ፤ አሁንም ህዝቦቿን ተሸክማ ሞስኮ ላይ በረረች (ከ85 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ተሸክሞ መብረር በጣም ከባድ ነው!)” አያችሁልኝ… የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች “እኛ ነን የተሸከምናችሁ” እያሉ ውለታ ለማስቆጠር ይሽቀዳደማሉ እንጂ እውነቱስ ሌላ ነው! እኔ የምላችሁ … ኢህአዴግ ስንት ሺ ካድሬ ሰብስቦ ስንት ዘመን “የአገር ገፅ ግንባታ” ሲለን የከረመውን አትሌቷ በ10 ሺ ሜትር ብቻ ገነባብታው መጣች አይደል! - ያውም በእግሯ! ወርቅ ማጥለቅ በለመደ የአቦ ሸማኔ እግሯ!! (ከአስር ሺ ካድሬ አንድ ጀግና አትሌት ይሏል ይሄ ነው!!)
ለአፍታ ወደ ሌላ አገራዊ አጀንዳ ልውሰዳችሁና ወደ አትሌቲክሱ እንመለስበታለን (አምዴ እንደ ኢቴቪ ማስታወቂያ የለውም!) በቅርቡ በኢቴቪ አንድ ውይይት (ግምገማ ቢባል ይሻላል) ተላልፎ ነበር - በህዳሴ ግድብ መዋጮና የቦንድ ግዢ ዙርያ፡፡ የቀድሞው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ሚኒስትር በነበሩት አቶ በረከት ስዩም የመድረክ መሪነት በተካሄደው ውይይት፣ ባለሀብቱ ለህዳሴው ግድብ ቃል የገባውን በመፈፀም ረገድ “ዳተኝነት” አሳይቷል ተብሏል፡፡ (በአጭሩ ቃሉን አልፈፀመም!) ባለሃብቱ በንፅፅር የቀረበው ደግሞ “ኑሮ ዳገት ሆኖበታል” ከሚባለው የመንግሥት ደሞዝተኛ ጋር መሆኑ ነገሩን አስገራሚ ያደርገዋል፡፡ እናም የደሞዝተኛውን ያህል እንኳን አስተዋፅኦ አላበረከተም የሚል ለዘብ ያለ ትችት ከመንግስት ወገን ተሰንዝሮበታል፡፡

ከዳያስፖራ ባለሃብት ጋር ቢወዳደርማ አለቀለት፡፡ አንዳንዱ ዳያስፖራ ሳልዘጋጅ ስለመጣሁ ነው እያለ ስንት እንደሚመዝ አይታችኋል? “ለጊዜው የ100ሺ ዶላር ቦንድ ገዝቻለሁ” እኮ ነው የሚለው! (ኢህአዴግ ዳያስፖራውን ጠበቅ ያድርግ!) በውይይቱ ላይ የተሳተፉት ባለሀብቶች የኢህአዴግ አባላት ስለመሆናቸው መረጃ የለኝም እንጂ … ከሆኑ እኮ የሰላ ግምገማ የግድ ነበር (ሂሳቸውን መዋጥ አለባቸዋ!) ምናልባት አድርባይነት ይሆን? ወይስ አፈንጋጭነት? የፈረደበት ኮንሰንሰስ ላይ ያለመድረስ (አገራዊ መግባባት ነው የሚሉት) ሊሆንም ይችላል፡፡ እኔ የምለው ግን … በ97 ምርጫ ማግስት የተቋቋመው “የኢህአዴግ ደጋፊዎች ነጋዴ ፎረም” የት ደረሰ? ወደ ሊግነት ተቀየረ እንዴ? (“የአርቲስቶች ሊግ” ተቋቋመ ሲባል ሰማሁ ልበል?) ባለሃብቶችና ያልተፈፀመ የህዳሴ ግድብ ቃላቸውን እያሰላሰልኩ ሳለ አንድ ድንገተኛ ሃሳብ ብልጭ አለልኝ (የፈጠራ እንዳይመስላችሁ!) እነዚህ በሙስና ተጠርጥረው የተያዙ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናትና ባለሃብቶች ለግድቡ አዋጥተዋል እንዴ? (ለጠቅላላ ዕውቀት ያህል ነው!) ምናልባት እኮ የ100ሺ ዶላር ባይሆን እንኳን የ100ሺ ብር ቦንድ ሸምተው ሊሆን ይችላል፡፡ ይሄ ደግሞ ድንገት ጥፋተኛ ከተባሉ ለብይን ማቅለያ ሳይጠቅማቸው አይቀርም (የአገር ፍቅር መገለጫ እኮ ነው!)
አሁን ወደ አትሌቲክስ እንመለስ፡፡

ወደ ስፖርቱ ሳይሆን ወደ ፖለቲካው አትሌቲክስ፡፡ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው ማንን መሰላችሁ? የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን ነው - እሱ ነዋ የቀለጠ ፖለቲካ አድርጐት ቁጭ ያለው፡፡ ስፖርት ነው ያሉትማ ወርቅ አጥልቀው የአገራቸውን ባንዲራ በስንት ሺ ኪ.ሜትሮች ርቀት ላይ እንዲውለበለብ አድርገዋል-በድላቸው!
እንደኔ ሰምታችሁ እንደሆነ ባላውቅም አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አንድ በዓይነቱ ለየት ያለ ማስፈራርያም ማስጠንቀቂያም የሚመስል መግለጫ አውጥቷል - በሞስኮው የሴቶች ማራቶን ውድድር አቋርጠው ለወጡት አትሌቶቻችንን! ውድድሩን አቋርጠው የወጡት አትሌቶች ምክንያታቸውን በፅሁፍ (በደብዳቤ) ለፌዴሬሽኑ እንዲገልፁ ተጠይቀዋል (ውድድር ማቋረጥ ወንጀል ሆነ እንዴ?) አይገርማችሁም … አትሌቶች ውድድር አቋርጠው የሚወጡት ለምን እንደሆነ የማያውቅ ፌዴሬሽን ነው ያለን (ፌዴሬሽን አይዋጣልንም ልበል?) እኔማ በጣም ስለገረመኝ ጥያቄውን መልሼ ለራሱ አቀረብኩለት - ለአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ፡፡ (ለአመራሩ ማለቴ ነው!) “እስቲ ገምቱ እነ ቲኪ ገላና ለምንድነው የሞስኮውን ውድድር አቋርጠው የወጡት?” ምናልባት ይሄ ጥያቄ ለፌዴሬሽኑ አመራሮች ጠጠር እንዳይልባቸው ፈራሁ (መጠየቅና መመለስ ለየቅል ናቸዋ!) እናም እስቲ ምርጫ ልስጣቸው (እንደ ት/ቤት ፈተና!)
ሀ- የአገር ፍቅር ስሜት በማጣት (ለግል ጥቅም በማድላት!)
ለ- ፌዴሬሽኑን ለማሳጣት (መልካም ስሙን ጥላሸት ለመቀባት)
ሐ- አገሪቱን ለማተረማመስ ከሚያስቡ ኃይሎች ጋር በማበር
መ- ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳ ካላቸው ኃይሎች ጋር “ጋብቻ” በመፈፀም
ሠ. መንግስትና ህዝብ ደስ እንዳይለው በማድረግ የግል ፍላጐታቸውን ለማርካት
ረ. ሁሉም መልስ ይሆናሉ
እርግጠኛ ነኝ በኢትዮጵያ የፈተና ታሪክ ብዙ ምርጫዎች የቀረቡበት ጥያቄ ይሄኛው ነው፡፡ ለነገሩ እኮ ደብዳቤ መፃፍ ቁም ነገር ሆኖ አይደለም (የፍቅር ደብዳቤ አይሁን እንጂ!) ግን ለምን እንዲህ በጥድፊያ አደረጉት? አንዱ ወዳጄ ምን አለኝ መሰላችሁ? “ያጣደፉትማ አትሌቶቹ ያቋረጡበትን ምክንያት እንዳይረሱት ብለው ነው” (ወረቀት የያዘው … ይባል የለ!) “ምን መሰለህ …” ብሎ ቀጠለ ወዳጄ “አየህ … ህመምና ስቃዩን ሳይረሱት በትኩሱ እንዲገልፁትም ብለው ነው” አለኝ፡፡ (የፌዴሬሽኑ ቃል አቀባይ የሆነ መሰለኝ!) በደርግ ዘመንም እንዲሁ ጀግናው አትሌት ምሩፅ ይፍጠር፤ በአንድ ውድድር ላይ ወርቅ ሳይሆን ብር አምጥቶ ወደ አገሩ ሲመለስ በመንግስት ባለስልጣን ተጠርቶ (ካድሬ በሉት!) ተግሳፅ ነገር ደርሶበታል የሚባል ነገር ሰምቻለሁ፡፡ (የደርግ ርዝራዦች ፌዴሬሽኑ ውስጥ አሉ ማለት ነው?) በእርግጥ የፌዴሬሽኑ አመራር የመላዕክት ስብስብ ነው ብዬ አላስብም (የአምባገነኖች መፈንጪያ ነውም አልወጣኝም!) ግን ፌዴሬሽኑ የስፖርት ሳይሆን የፖለቲካ ፓሽን ባላቸው ግለሰቦች ሳይሞላ አልቀረም፡፡

የፌዴሬሽኑ ፖለቲካ ግን ይሄ ብቻ እንዳይመስላችሁ፡፡ በ10ሺ ከዓለም በአንደኝነት ደረጃ ላይ የምትገኘውና በ5ሺ ደግሞ በሁለተኝነት ላይ ያለችው ጀግናዋ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በ5ሺ ውድድር እንዳትካፈል ተደርጋለች - የማሸነፍ ብቃት እንዳላት እየታወቀ! ለምን አትሉም? ለተተኪዎች እድል ለመስጠት በሚል ተልካሻ ምክንያት!! እንዴ… ተተኪዎች እሷ የደረሰችበት ደረጃ ላይ መድረስ ያለባቸው በኮታ ነው በብቃት? ጥሩነሽ እኮ ለዚህ የበቃችው አርአያ የሆኗት እነደራርቱ “ተተኪ ነሽ” ብለው እድል ስለሰጡዋት አይደለም፡፡ በብቃቷ አሸንፋና ልቃ ነው!! ቀነኒሳም አርአያዬ የሚለውን አትሌት ኃይሌን አሸንፎ ነው ለዛሬው ስኬት የበቃው፡፡ እናም ስፖርት እንደ ፖለቲካ አይደለም - በችሮታና በምፅዋት አይገኝም (ብቃትና ልቀት ነጥሮ የሚወጣበት ነው!) ምናልባት የምፈራው ምን መሰላችሁ? የፌዴሬሽኑ አመራር የኢህአዴግን የመተካካት ስትራቴጂ በቀጥታ ቀድቶ እየተገበረ እንዳይሆን? (ጥርጣሬ እኮ ነው!) ምን ትዝ እንዳለኝ ታውቃላችሁ? የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር (ነፍሳቸውን ይማረውና) አንዴ ወጣቶችን ሰብስበው ሲያወያዩ “ሥልጣን ማንም የሚሰጣችሁ የለም! ራሳችሁ ናችሁ መውሰድ ያለባችሁ!” ብለው ነበር (ፌዴሬሽኑ አልተዋጠለት ይሆን?) ወጋችንን ከፌስ ቡክ ላይ በተገኘ የሳምንቱ ምርጥ ጥቅስ እንቋጭ፡-
“ሥራችሁን በፍፅምና ስታከናውኑ ያኔ ጥሩነሽ ዲባባ ትባላላችሁ” ከዚህ በተቃራኒው ሲሆን ደግሞ (እቺኛዋ የእኔ ናት!) የኢትየጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን ሆናችሁ ማለት ነው፡፡

  • የፀረ ሽብር ህግ ጭራሽ አይኑር የሚል አቋም የለንም 
  • በፀረ ሽብር ሕግ ሰበብ ዜጐች እንዳይደራጁ እየተደረገ ነው
  • መተካካት የኢህአዴግ አጀንዳ ነው፤ እኛ የወጣቶች ማህበር አይደለንም

አንድነት ለፍትህ እና ለዲሞክራሲ የሦስት ወር መርሃ ግብር ቀርፆ፣ በተለያዩ የሃገሪቱ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፎችና ህዝባዊ ስብሰባዎችን እያደረገ ነው፡፡ “የሚሊዮኖች ድምፅ” በሚልም የፀረ ሽብር ህጉን ለማሰረዝ ፊርማ የማሰባሰብ እንቅስቃሴ መጀመሩ ይታወቃል፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ፤ አክራሪነትና ሽብርተኝነት በሚሉት ጉዳዮች የአንድነት አቋም ምንድነው? የፀረ ሽብር ህጉ እንዲሰረዝ ለምን ተፈለገ? በእነዚህና ተያያዥ በሚሉና ተያያዥ ርእሰ ጉዳዮች ዙርያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ከፓርቲው ሊ/መንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ጋር ያደረገውን ቃለምልልስ እንደሚከተለው አጠናቅረነዋል፡፡

 በአሁኑ ሰዓት አንድነትን ጨምሮ የተቃዋሚዎች ተከታታይ ሰልፍ መጥራት የ8 አመቱን እገዳ ማካካስ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?

እርግጥ ከ97 በኋላ ትላልቅ ሰላማዊ ሰልፎች አልተካሄዱም፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ከ97 በፊት የነበሩትን ሰላማዊ ሰልፎች ያደራጅ የነበረው ፓርቲ (ቅንጅት) መከፋፈል ነው፡፡ ያ ክፍፍል ከተፈፀመ በኋላ ቅንጅትን እንደገና ማደራጀት አልተቻለም፡፡ ስለዚህ ሁሉም በራሱ አካሄድ እንደገና መደራጀት ውስጥ ገባ፡፡ ሰፊውን ጊዜ የወሰደው በቅንጅት የነበረውን መንፈስ ይዞ መቀጠል የሚያስችል አደረጃጀትን የመፍጠር ጉዳይ ነበር፡፡ እስከ 2001 ዓ.ም ድረስ በዚህ አካሄድ ከቆየን በኋላ ምርጫ መጣ፡፡ በምርጫው ተሳተፍን፡፡ ቀጥሎም ምርጫውን መገምገም ነበረብን፡፡ ምርጫውን ከገመገምን በኋላ ከዚያ ተነስተን የ5 አመት ስትራቴጂ ማውጣት ነበረብን፡፡

በትክክል እኛ ስራ ጀምረናል የምንለው በ2004 ዓ.ም ነው፡፡ የትግል ስልታችን ሰላማዊ ነው፡፡ ሌላ የትግል ስልት የለንም፡፡ የዚህ የትግል ስልት አንዱ መገለጫው ደግሞ ህዝባዊ ስብሰባዎችንና ሰላማዊ ሰልፎችን ማካሄድ ነው፡፡ ነገር ግን በወቅቱ በወጡት አዋጆችና የተለያዩ ክልከላዎች ሳቢያ እነዚህን ስልቶች ተግባራዊ ለማድረግ ፈታኝ ሆኖብን ነበር፡፡ በሌላ በኩል ፓርቲው አዳዲስ አደረጃጀቶችን በመፍጠር ሂደት ውስጥ ነበር፡፡ ለአባላቱም ስለ ሰላማዊ ትግል ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ከዚያ በኋላ በስፋት ህዝባዊ ንቅናቄዎችን መፍጠር ጀመርን ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እኛ ለማካካስ ሳይሆን በእቅዳችን ነው ስንጓዝ የነበረው፡፡ እዚህ ላይ ለማስታወስ የምፈልገው ትላልቅ ሰላማዊ ሰልፎች ባይካሄዱም ቀደም ብሎ ወ/ት ብርቱካን እንድትፈታ ሰላማዊ ሰልፍ አድርገን ነበር፡፡
አሁን እያካሄዳችሁት ያለው ሰላማዊ ሰልፍ በትክክል የታቀደበት ነው?
አዎ! እቅዱን የነደፍነው ከሚያዝያ 2005 ጀምረን ነው፡፡ እቅዱን እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደምንችል ስንወያይ ቆየን፡፡ ከዚያም እንቅስቃሴውን ለሦስት ወራት እናካሄዳለን ብለን ፕሮግራም አወጣን፡፡ ሰኔ፣ ሐምሌ እና ነሐሴ ወር ላይ ለማካሄድ ወሰን፡፡ በሁለት ምክንያቶች ነው ይህን ወቅት የመረጥነው፡፡ አንደኛ የአመቱ ማጠቃለያ ስለሆነ በአመቱ አንዳች ስራ ለመስራት ሲሆን ሌላው ቀጣዩ ጠቅላላ ጉባኤ የሚካሄደው በመስከረም ወር ነው፡፡ ስለዚህ ከዚያ በፊት የሦስት ወር ፕሮግራም ነድፈን በደንብ የተዘጋጀንበት እንጂ ዝም ብለን የጀመርነው አይደለም፡፡
የሰልፉ አላማ ወይም ከሠልፉ የሚጠበቀው ውጤት ምንድን ነው?
ከሰልፉ ብቻ ሳይሆን ከእቅዳችን የምንጠብቀው፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት ለመፈፀሚያ አመቺ የሆነው ወይም አሁን እንደምናየው ፖለቲከኞችን፣ ጋዜጠኞችን እና ሌሎች የህብረተሰቡ አካሎችን ለማጥቂያ ጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኘው የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ እንዲሻሻል ወይም ከነጭራሹ እንዲሰረዝ የሚል ነው፡፡ ይህ እንዲሆን ህጉ ምን አይነት እንደሆነ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ምን አይነት ጉዳት እያደረሰ እንዳለ ህዝቡ እንዲረዳው እንፈልጋለን፡፡ ከሰልፉ ባሻገር የህብረተሰቡን ድጋፍ አሰባስቦ ለሚመለከተው አካል ህጉ ወይ ይሻሻል አሊያም ይሰረዝ የሚል ማመልከቻ ማቅረብ ነው፡፡ ይህን ህግ በመቃወም ሚሊዮኖች ከፈረሙ ተሰሚነት ያገኛል በሚል ነው እንቅስቃሴውን የጀመርነው፡፡ በዚህ ብቻ አናበቃም፡፡ ስለፓርቲውም ስለ ህጉም የተለያዩ መረጃ ሰጪ በራሪ ወረቀቶች እንበትናለን፡፡ ሌላው በእንቅስቃሴ ውስጥ አባላትን ማፍራት ይቻላል፡፡ በዚህ እንቅስቃሴ ልናተርፈው የምንችለው እንግዲህ እነዚህ ናቸው፡፡
የምታካሂዱት እንቅስቃሴ በመንግስት ላይ ጫና ፈጥሮ ህጉን የማስቀየር አቅም ይኖረዋል? ወይም የዚያን ያህል አቅም እንዲኖረው አድርጋችሁ ነው እየተንቀሳቀሳችሁ ያላችሁት?
መንግስትም፣ ዜጐችም፣ የአለም ማህበረሰብም እንዲያውቅ የምንፈልገው በዚህ በፀረ ሽብርተኝነቱ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የኑሮ ጉዳዮችም ህዝቡ መተንፈሻ ይፈልጋል፡፡ በየጊዜው በሚደረጉት ሰልፎችና ስብሰባዎች የሚወጣው ህዝብ ምን ያህል እንደሆነ በሚያይበት ጊዜ በሚዲያም ሲስተጋባ በሚመለከተው አካል ላይ ተጽእኖ ይፈጥራል፡፡ በአንድ በኩል ህዝቡ የታመቀ ብሶቱን እንዲገልጽ ያስችላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ይሄ ጉዳይ ለካ የህዝብም ጥያቄ ነው ብሎ መንግስት ቆም ብሎ እንዲያስብ ይረዳል፡፡ ሌሎችም የመንግስት የገቢ ምንጭ አካላትም በመንግስት ላይ ተጽእኖ እንዲፈጥሩ ይረዳል፡፡ መንግስት ግትርነቱን ትቶ የህዝቡን ድምጽ መስማት ይጀምራል ወይ የሚለው ሌላ ጥያቄ ነው፡፡ በመሠረቱ ይህን እንቅስቃሴ ስናደርግ መንገዱ አልጋ በአልጋ ሆኖ አይደለም፡፡ ሌሎች አካባቢዎች በብዙ ውጣውረድ ፍቃድ አግኝተን አላማችንን ብናሳካም በትግራይ መቀሌ እና በወላይታ ሶዶ ከአስተዳደሩ ጀምሮ እስከታች ወረዳ ድረስ ያሉ አመራሮች እርስ በእርስ በመጠላለፍ በሰሩት ስራ ያሰብነውን ማካሄድ አልቻልንም፡፡
ምን ነበር በሁለቱ ቦታዎች ያሰባችሁት?
መቀሌ ላይ ሰላማዊ ሰልፍ ነበር ያቀድነው፡፡ ወላይታ ሶዶ ደግሞ ህዝባዊ ስብሰባ ነበር፡፡ ሁለቱም ተጨናግፈውብናል፡፡ ከላይ ጀምሮ እስከታች ድረስ በነበረው አሻጥር እቅዳችን ሊሣካ አልቻለም፡፡
አክራሪነትና ሽብርተኝነት በሚባሉት ጉዳዩች ላይ “አንድነት” ያለው ጥርት ያለ አቋም ምንድን ነው?
እኛ ሽብርተኝነትን በጥብቅ እንቃወማለን፡፡ ሽብርተኝነት ምን ማለት ነው በሚለው ላይ በህገመንግስቱ መሠረት ነው የምንሄደው፡፡ በአንቀጽ 29 መሠረት ሰዎች የፈለጉትን ሃሳብ መያዝ ይችላሉ፡፡ በሚዲያ አማራጮችም መግለጽ ይችላሉ፡፡ ይህ መብት በህገመንግስቱ ተደንግጓል፡፡ ይሁን እንጂ የፀረ ሽብር ህጉ ይህንን አንቀጽ የሚጥስ ነው፡፡ ገና አስበዋል ተብሎ በተግባር ያልፈፀሙ ወይም ለመፈፀም ዝግጅት ባላደረጉ ሰዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው፡፡ ሁለተኛ በህገ መንግስቱ በአንቀጽ 30 ላይ ማሰብ ብቻ ሳይሆን ህዝባዊ ስብሰባዎችንና ሰላማዊ ሰልፎችን በማድረግ ያልመሰለህን ነገር መቃወምና እንዲሻሻል ለመንግስት ማመልከቻ ማቅረብ ይቻላል፡፡ ነገር ግን ይህም መብት እየተጣሰ ነው፡፡ ሌላው በዚህ የፀረ ሽብር ህግ በማሳበብ ዜጐች እንዳይደራጁ እየተደረገ ነው፡፡ እነዚህን ህገመንግስታዊ የመብት ጥሰቶች እኛ አጥብቀን እንቃወማለን፡፡ በዚህ አካሄድ የታሰሩ ሰዎች እንዲፈቱም ነው እንቅስቃሴ የምናደርገው፡፡ አስረግጬ መናገር የምንፈልገው እኛ እውነተኛ ሽብርተኝነትን አጥብቀን እንቃወማለን፡፡
አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የሽብርተኝነት ስጋት አለ ብላችሁ ታምናላችሁ?
በምንድን ነው የምናረጋግጠው? መንግስት በሚለው ብቻ እንጂ የምናውቅበት መንገድ የለም፡፡
ለምሣሌ አዲስ አበባ ውስጥ የደረሱ የቦንብ ፍንዳታዎች በማሳያነት ይቀርባሉ?
እሱ ቆይቷላ! እንደዚያ አይነት ነገር በ2004 ዓ.ም የታለ? የዚያ አይነት ፍንዳታ አላየሁም፡፡ አንዳንድ አካባቢዎች በሰዎች አለመግባባት ግጭቶች ተፈጥረው ሊሆን ይችላል እንጂ ሽብርተኝነት በጉልህ ለመኖሩ እኛ መረጃ የለንም፡፡
መንግስት፤ የሃይማኖት አክራሪነት የሃገሪቱ ስጋት ነው ሲል ይገልፃል፡፡ በእናንተ በኩል ይህን እንዴት ነው የምትመለከቱት?
አክራሪነት አንድ ሰው አንድ ሃሳብን ይዞ የማክረር ጉዳይ ነው፡፡ እኛ በግምገማችን ሰዎች ስለመብታቸው መከበር እየጠየቁ መሆናቸውን፣ ይህን በማድረጋቸው መታሰራቸውን ደርሰንበታል፡፡ ይህን በማድረጋቸው ደግሞ መታሰር የለባቸውም፡፡ ለምሣሌ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ፤ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተማረኝ እንደዚህ ነው፣ ይሄ መሆን አለበት ብሎ በሌሎች ላይ ጫና የመፍጠር ሁኔታ እኔ አላየሁም፡፡ የግራ ፊትህን ለመታህ ቀኝህንም ስጠው በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ መርህ የሚሄዱ አሉ፤ ቁርአን ይሄን ይሄንን ነው የሚለው ስለዚህ በዚህ መንገድ ነው መሄድ ያለብን ብሎ የሚያስተምርም አለ፡፡ ያንን ሃሳብ የመያዝና የማስተማር መብቱ በአንቀጽ 29 እና 31 (በህገ መንግስቱ) የተጠበቀ ነው፡፡
መንግስት፤ አንዳንድ ተቃዋሚዎች “እስላማዊ መንግስት” እንዲመሠረት ከሚሹ አክራሪ አካላት ጋር እየሰሩ ነው ይላል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የእናንተ አቋም ምንድነው?
የእስላማዊ መንግስት ቢቋቋም ጥሩ ነው የሚል ካለ፣ ያንን ለምን አሰብክ ብሎ መጋፋት ትክክል አይደለም፡፡ መብቱ ነው፡፡ ያንን በተለያዩ መንገዶች ተግባራዊ ለማድረግ የሚንቀሳቀስ ከሆነ ነው ችግሩ፡፡ ምክንያቱም የሌሎቹን መብት እየተጋፋ ነው ማለት ነው፡፡ እኛ እስካሁን ድረስ ይሄን አላየንም፡፡ እስላማዊ መንግስት በኢትዮጵያ ይቋቋም የሚል ጥያቄ አንስቶ የሚንቀሳቀስ ስለመኖሩ እኔ እስካሁን አልሰማሁም፡፡
አንድነት የፀረ ሽብርተኝነት ህግ ያስፈልጋል የሚል እምነት አለው?
በአንድ በኩል ወንጀሎች ናቸው እየተፈፀሙ ያሉት፡፡ ለዚያ ደግሞ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ አለ፡፡ እዚያ ላይ የሚጐድል ነገር ካለ ማሻሻል ይቻላል፡፡ እንዳልኩህ ሽብርተኝነትን እንቃወማለን፡፡ በዚያ አካሄድ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን እንቃወማለን፡፡ ካስፈለገ ህግ ሊወጣ ይችላል፡፡ እኛ የፀረ ሽብርተኝነትን ህግ ጭራሽ አይኑር የሚል አቋም የለንም ግን የሚወጣው ህግ ዜጐችን መልሶ የሚጐዳ መሆን የለበትም፡፡
ይሄን ጥያቄ ያነሳሁት አሁን ከጀመራችሁት እንቅስቃሴ አንዱ የፀረ ሽብር አዋጁን ማሠረዝ ስለሆነ ነው?
አዎ እኛ የፈለግነው በ2003 የወጣው አዋጅ እንዲሠረዝ ነው፡፡ ያ አዋጅ በዜጐች ላይ መልሶ ጥቃትን የሚፈፅም አዋጅ ነው፡፡ ጥሩ አይደለም፡፡ ይሄ የ2003 አዋጅ ወይ ይቀየር ወይም ተሻሽሎ ይውጣ ነው እንጂ ያልነው የፀረ ሽብር ህግ ከነጭራሹ አያስፈልግም አላልንም፡፡
አንድነትን ጨምሮ የሃገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች የአመራርነት ቦታ ለተተኪ ወጣቶች እድል የሚሠጥበት አይደለም ይባላል፡፡ በዚህ ላይ የእርሶ አቋም ምንድነው?
መተካካት የኢህአዴግ አጀንዳ ነው፡፡ እኛ የፖለቲካ ፓርቲ እንጂ የወጣቶች ማህበር አይደለንም፣ ወይም ደግሞ የሴቶች ማህበር አይደለንም፡፡
ወጣቶችም ይሁኑ ሽማግሌዎች ወይም ሴቶችና ሠራተኞችም ይሁኑ ዋናው ቁም ነገር የፖለቲካ ጉዳይ ነው፡፡ አላማችንን አይቶ በፍላጐት ለመታገል የመጣን ሰው ወጣት አይደለህምና አይሆንም ብለን አናገልም፡፡ የአመራር ብቃት የሚታየው በእንቅስቃሴ ውስጥ ነው፡፡ በተጨባጭ ግን እንደማየው የአንድነት ፓርቲ አመራር በአብዛኛው በወጣቶች የተደራጀ ነው፡፡ እኔና አቶ አስራት ብቻ ነን ወደ 70 የተጠጋነው (እየሳቁ) የተቀረው ከዚያ በታች ነው፡፡
በእርግጥ የዚምባቡዌው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤም ሰሞኑን በ89 ዓመታቸው ለ7ኛ ጊዜ በምርጫ ተወዳድረው ማሸነፋቸውን ሰምተናል…
ጥያቄው ሰውየው መንቀሳቀስ ይችላል ወይ ነው፡፡ ማሰብ ይችላል ወይ ነው፡፡ ወይስ አርጅቶና ጃጅቶ የማይሆን ተግባር ይፈጽማል ወይ ነው መሆን ያለበት፡፡ ለመምራት እውቀቱ ያስፈልጋል፣ ጤንነት ያስፈልጋል፡፡ በአካል የመንቀሳቀስና በአዕምሮው በሚገባ ማሰብ የሚችል ሰው መሆን አለበት፤ ያ ከሆነ ጥሩ ነው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ አንድ መሪ ብቻውን አይደለም ሀገር የሚመራው፡፡ ስለዚህ የግድ ወጣቶች ብቻ መሆን የለበትም፡፡
ከመኢአድ ጋር ውህደት ለመፍጠር በድጋሚ እንቅስቃሴ መጀመራችሁ እየተነገረ ነው፡፡ ምን ላይ ደረሳችሁ?
በ2004 ዓ.ም ኮሚቴ አቋቁመን ነበር፡፡ እኛ ከመድረክ ጋር አስቀድመን ግንባር ፈጥረናል፤ ይሄን በማይነካ መልኩ ከመኢአድ ጋር ውህደት ለመፍጠር ሲንቀሳቀስ የነበረ ኮሚቴ አቋቁመን መነጋገር ጀምረን ነበር፡፡ ግን በአንድ ጉዳይ ምክንያት መስማማት አልቻልንም፤ መኢአድ የብሔር ድርጅቶችን የጐሣ ድርጅቶች ናቸው ይላል፡፡ ከነዚህ ድርጅቶች ጋር ለመስራት አልፈልግም የሚል አቋም አለው፡፡ አንድነት መድረክ ውስጥ እስካለ ድረስ ውህደት ሊኖር እንደማይችልም አቋሙን አስረግጦ ገልጿል፡፡ እኛ ደግሞ መድረክ ውስጥ የገባንበት ምክንያት አለን፡፡ ስለዚህ ከእናንተ ጋር ለመዋሃድ ብለን ከመድረክ የምንወጣበት ምክንያት የለም ብለናቸዋል፡፡ ምርጫ 2005 የፈጠረው የ33 ፓርቲዎች ትብብር ውስጥም ሁለቱም ፓርቲዎች አሉ፡፡ በዚያ በኩል አብሮ ተባብሮ ለመስራት የተፈረመ ስምምነት አለ፡፡ ከዚያ ውጪ በተናጠል የጀመርነው ነገር የለም፡፡ በግለሰብ ደረጃ ውይይቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በመዋቅር ደረጃ ግን በ2004 ተሞክሮ አልተሳካም፡፡
በሌላ በኩል ከመድረክ ጋርም ግንኙነታችሁ እየሻከረ መሆኑ እየተነገረ ነው…
ግለሰቦች ነፃነት አላቸው፡፡ አንዳንዴ ችግር የሚፈጠረው በፓርቲ ውስጥ ያለ ግለሰብ በግሉ ሃሳብ በሚያቀርብበት ጊዜ የፓርቲው አቋም ነው ብለው የሚወስዱ አሉ፡፡ ለምሣሌ እነ አቶ ቡልቻ በግለሰብ ደረጃ የሚናገሩት አለ ያ ማለት የመድረክ አቋም አይደለም፡፡ ፕ/ር በየነ በአቶ ግርማ ላይ ይጽፋሉ፤ አቶ ግርማም ይመልሳሉ፣ ይሄ የግለሰቦች ጉዳይ ነው፡፡ ምናልባት አንድነት የ4 አመት ጉዟችንን ገምግሞ ነበር፡፡ ከመድረክ ጋር ያለን ግንኙነት እንዴት ነበር? አብሮ በመስራት ምን ውጤት ተገኘ? የሚል ግምገማ አካሂደን ነበር፡፡ በዚያ ምክንያት በአካሄድ ጉዳይ ላይ ንግግሮች ነበሩ፡፡ ከዚህ ውጪ በአንድነትና በመድረክ መካከል ምንም ችግር የለም፡፡ ችግርም ካለ በህገ ደንባችን መሠረት የሚፈታ ይሆናል፡፡
በውጭ አገር ያሉት ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ እና አቶ ስዬ አብርሃ አሁንም የአንድነት አባል ናቸው?
አቶ ስዬ ከዚህ ሲሄድ አባል ነበረ፡፡ አሜሪካን ከሄደ በኋላም አለቀቀም፤ ሲረዳን ነበር፡፡ በእርግጥ አንዳንድ ፓርቲውን ለቋል የሚሉ ሃሜታዎች ይሰማሉ፡፡ ነገር ግን ከአቶ ስዬ በኩል በዚህ ምክንያት ፓርቲውን ለቅቄያለሁ የሚል ደብዳቤ አልደረሰንም፡፡ እንደሚወራው ከሆነ በፖለቲካ ስራ ላይ እንዲሳተፍ የማይፈቅድለት ስራ ውስጥ ተቀጥሯል፡፡ ይሄንን ግን አሜሪካ ቦስተን ያለው ወኪላችን አላረጋገጠልንም ወይም አቶ ስዬ ራሱ ምክንያቱን አስረድቶ አላሳወቀንም፡፡ አሁን ላይ ሆኜ ስለሱ ምንም ማለት አልችልም፡፡ ወ/ት ብርቱካንን በተመለከተ ግን አባላችን ብቻ ሳይሆን ሊቀመንበራችንም ነበረች፡፡ ወደ አሜሪካ ከመሄዷ አንድ ቀን በፊት በአንተ በኩል መልዕክት እንዲደርስልኝ እፈልጋለሁ ብላኝ ተገናኘን፡፡ በእስር ቤት ከደረሰባት ጫና ለማገገምና ለትምህርት እንደምትሄድ አስረድታኝ የአንድነት ፓርቲ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ከእንግዲህ አልኖርም ብላ በግልጽ ነግራኛለች፤ ስለዚህ አባላችን አይደለችም፡፡
አትሌት ሀይሌ ገ/ስላሴ በ2007 ፓርላማ ለመግባት እንደሚወዳደርና በቀጣይም ፕሬዚዳንት ለመሆን እንዳሰበ በይፋ ተናግሯል፡፡ እርስዎ በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት? በሁለቱም ሂደቶች ያለፉ ስለሆኑ ነው ጥያቄውን ያነሳሁት…
እዚህ ላይ ወይ የሱ አሊያም የሰዎች የግንዛቤ ችግር አለ፡፡ የፓርላማ ምርጫ በ2007 ነው፡፡ አዲስ ፕሬዚዳንት የሚሾመው በ2006 መስከረም ወር ነው፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ ከፈለገው ፓርላማ ሳይገባ ከውጪ ለፕሬዚዳንትነት እጩ አድርጐ ሊያስመርጠው ይችላል፡፡ ህገመንግስቱ አንድ ፕሬዚዳንት ተደርጐ የተመረጠ ሰው የፓርላማ አባል ከሆነ ወንበሩን መልቀቅ አለበት ይላል፡፡ ያ ማለት ከፓርላማም ከውጪም ሊመጣ ይችላል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ፕሬዚዳንት መሆን ከፈለገ አሁን ነው እጩ መሆን የሚቻለው፡፡