በምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ (ሴካፋ)የክለቦች ሻምፒዮና ካጋሜ ካፕ ዛሬ በዳሬሰላም ዛሬ ይጀመራል። ኢትዮጵያን ወክሎ በሻምፒዮናው ታሪክ በተከታታይ ዓመት ለሁለተኛ ጊዜ የሚሳተፈው አዳማ ከነማ ሲሆን በ21 ተጨዋቾች የመጨረሻ ዝግጅቱን አከናውኖ ወደ ታንዛኒያ ያቀናል፡፡ በዞኑ የክለቦች ሻምፒዮና ላይ በመጨረሻው ሰአት ተሳታፊ መሆኑን ያወቀው ክለቡ ከውድድር ዘመኑ ማለቅ ተያይዞ በተከፈተው የዝውውር መስኮት ሙሉ ቡድኑን አልያዘም፡፡ አዳማ ከነማ የካጋሜ ካፕ ከመጀመሩ በፊት ከስብስቡ ወሳኙን አጥቂ በረከት አዲሱን ጨምሮ ውላቸውን የጨረሱ በርካታ ተጨዋቾችን ቢያጣም በተከፈተው የዝውውር መስኮት 7 አዳዲስ ተጫዋቾች ከቡድኑ ጋር አዋህዶ ለመስራት ጥረት ማድረጉን የመረጃ ምንጮች አውስተዋል፡፡  ከዝግጅቱ ጎን ለጎንም የወዳጅነት ጨዋታ ከሰበታ ከነማ ክለብ ጋር በማድረግ 1 እኩል አቻ የተለያየ ሲሆን ዋና  አሰልጣኙ አሸናፊ በቀለ ክለባቸው በምድብ ጨዋታዎች ጥሩ ተሳትፎ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
በ2007 ዓም የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ጥሩ ተፎካካሪ ሆኖ በሶስተኛ ደረጃ የጨረሰው አዳማ ከነማ በካጋሜ ካፕ ላይ በምድብ 3 ከታንዛኒያው አዛም ፤ ከዩጋንዳው ኬሲሲ እንዲሁም ከደቡብ ሱዳኑ ማላኪያ እንደተደለደለ ይታወቃል፡፡ የ2014 የታንዛኒያ ፕሪሚዬር ሊግ አሸናፊ የሆነው አዛም ለካጋሜ ካፕ ያደረገውን ዝግጅት ለመፈተሽ ሰሞኑን  ከሁለቱ የአገሪቱ ክለቦች አፍሪካን ስፖርትስ እና ኮስታልዩኒዬን ጋር ተጫውቶ በ1ለ0 ተመሳሳይ ውጤት አሸንፏቸዋል፡፡ በ1978 የካጋሜ ካፕን ያሸነፈው የኡጋንዳው ኬሲሲ ቡድን የቀድሞ ተጨዋች ለክዋዎስፖርት ድረገፅ በሰጠው አስተያየት በምድብ 3 ከሚገኙ ቡድኖች ለማይታወቀው እና በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ከቅዱስ ጊዮርጊስ እና ከደደቢት ጋር ተፎካካሪ ለነበረው አዳማ ዝቅተኛ ግምት መስጠት እንደማይገባ ተናግሯል፡፡ ዋና አሰልጣኙ በበኩላቸው ዋንጫውን ለማሸነፍ እቅድ አለን ብለዋል፡፡ በምድብ 3 ከተደለደሉ ክለቦች ተጨዋቾች የኬሲሲው ቶም ማሲኮና ጆሴፍ ኦቻያ እንዲሁም ከታንዛኒያ ሻምፒዮን አዛም ጆን ራፌል ባኮና ኪፕሬ ቴቼ በሻምፒዮናው ምርጥ ብቃት በማሳየት ጎልተው ይወጣሉ ከተባሉ ተጨዋቾች ግንባርቀደም ተጠቃሾቹ ናቸው፡፡

ለዓመታት ዋጋው ዝቅና ከፍ እያለ ሲያማርረን ከርሞ፣ ዛሬ ዋጋው ብቻ ሳይሆን ገበያ ውስጥ አለመገኘቱ የሚያስጨንቀን ስኳር፣ በጤናችን ላይ ቀላል የማይባል መዘዝ እንደሚያስከትል የሥነ ምግብ ተመራማሪዎች ይገልፃሉ፡፡
ለመሆኑ ይህንን ዋጋው ጣራ ከመንካቱም በላይ እንደ ልባችን መሸመት ያልቻልነውን ስኳር ባንጠቀም ምን ይቀርብናል?
የሥነ ምግብ ባለሙያዋ ወ/ሮ ህሊና ታደሰ እንደሚናገሩት፤ ለሰውነታችን አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን በምንገባቸው ምግቦችና መጠጦች ውስጥ በበቂ መጠን የምናገኝ በመሆኑ ተጨማሪ ስኳር ለምግብነትና ለመጠጥነት በምንጠቀምባቸው ነገሮች ውስጥ መጨመሩ በሰውነታችን ውስጥ ከአስፈላጊ መጠን በላይ የሆነ ስኳር እንዲጠራቀም ያደርገዋል፤ይህ ደግሞ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እጅግ ያመዝናል፡፡  
ለምግብነትም ሆነ ለመጠጥነት በምንጠቀምባቸው ነገሮች ውስጥ ስኳርን አለመጨመራችን የጣዕም ቀማሽ ህዋሳቶቻችንን ስሜት ለተወሰነ ጊዜ ቅር ከማሰኘት የዘለለ ጉዳት እንደሌለው የሚናገሩት ባለሙያዋ፣ የምንወስደውን የስኳር መጠን እየጨመርን በሄድን ቁጥር ከመጠን ላለፈ የክብደት መጨመር፣ ለስትሮክ፣ ለስኳር ህመምና ሌሎች በጤና ላይ ከባድ ችግር ለሚያስከትሉ በሽታዎች የመጋለጥ ዕድላችንም እየጨመረ እንደሚሄድ ጠቁመዋል፡፡
የሥነምግብ ተመራማሪዎች ስኳርን እጅግ አደገኛ በሆኑ አራት ትላልቅ ምድቦች ይከፍሉታል፡፡ አነዚህም ሱክሮስ፣ ፍሩክቶስ፣ የማር ስኳርና የብቅል ስኳር እየተባሉ የሚጠሩት ናቸው፡፡
ሱክሮስ
ለቤት ውስጥ ፍጆታ የምናውለው፣ ሻይ ቡናን ለማጣፈጥ የምንጠቀምበትና አሁን ገበያ ውስጥ እንደልብ ልናገኘው ያልቻልነው ስኳር ነው፡፡ ይህ የስኳር ዓይነት ምንም ዓይነት ቫይታሚንም ሆነ ማዕድን የሌለው ሲሆን ይህንን የስኳር አይነት ባለመጠቀማችን በሰውነታችን ላይ የሚያስከትልብን የጤና ችግር የለም፡፡ ይልቁንም ይህንን የስኳር አይነት አብዝተን መጠቀማችን ለሞት ሊዳርጉን ለሚችሉ ከባድ የጤና ችግሮች ሊያጋልጠን እንደሚችል የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡  
ፍሩክቶስ
በአትክልቶች ውስጥ የሚገኝና የደም ውስጥ ቅባትን በመጨመር የሚታወቅ ነው፡፡ ይህ የስኳር አይነት በመጠኑ ከተወሰደ ለጤና ጠቃሚ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን ይዟል፡፡ ከመጠን ካለፈ ግን ችግር ማስከተሉ የማይቀር ነው፡፡ ህፃናትና ሰውነታቸው በበሽታና በልዩ ልዩ ምክንያቶች የተጐዱ ሰዎች የዚህ ዓይነቱ ስኳር በመጠኑ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ኃይል፣ አቅምና ብርታትንም በመስጠት ይታወቃል፡፡
የማር ስኳር
ይህ የስኳር ዓይነት በማር ውስጥ የሚገኝ ሲሆን የስኳር ይዘቱም እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ በአንድ ማንኪያ ማር ውስጥ 65 ካሎሪ ይገኛል፡፡ ተመሳሳይ መጠን ባለው ስኳር ውስጥ የሚገኘው የካሎሪ መጠን ግን 48 ብቻ ነው፡፡ ይህ የስኳር ዓይነት በመጠኑ ሲወሰድ የሰውነታችን አቅም ይጨምራል፣ እርጅናን ይከላከላል (የሰውነታችን ሴሎች ሥራቸውን በአግባቡ ለማከናወን እንዲችሉ ያደርጋቸዋል) በሌላ በኩል መጠኑን ያለፈ የማር ስኳር የበሽታ ምንጭ ይሆናል፡፡  
የብቅል ስኳር
በጥራጥሬዎች መብላላት ውስጥ የሚገኝና ከፍተኛ የስኳር ይዘት ያለው የስኳር ዓይነት ነው፡፡ ይህ ስኳር በሰውነታችን ውስጥ የሚገኙ ኢንዛይሞችና ቫይታሚኖችን በመምጠጥ ሰውነታችንን ያዳክመዋል፡፡ ብዙውን ጊዜ ብቅል ነክ በሆኑ ነገሮች የተሠሩ መጠጦችን አብዝተው የጠጡ ሰዎች ሰውነታቸው ሲደክምና ሲገረጣ የሚታየው በመጠጡ ውስጥ ያለውና በብቅል (በጥራጣሬዎች) መብላላት ሳቢያ የሚፈጠረው ስኳር በሰውነታቸው ውስጥ ያሉ ኢንዛይሞችን በመምጠጥ ስለሚያዳክማቸው ነው፡፡
የሥነምግብ ባለሙያዋ እንደሚናገሩት፤ በለስላሳ መጠጣችንም ሆነ ብቅል ነክ በሆኑ ነገሮች ተሠርተው ጥቅም ላይ የሚውሉ መጠጦችን አዘውትሮ መጠቀም ጤንነትን በእጅጉ የሚጐዳ ነው፡፡ በአንድ ጠርሙስ የለስላሳ መጠጥ ውስጥ 10 ማንኪያ ስኳርና 150 ካሎሪ እንደሚገኝ የጠቆሙት ባለሙያዋ፤ አንድ ሰው በቀን ከ12 ማንኪያ በላይ ስኳር መጠቀም እንደሌለበት ተናግረዋል፡፡
እየጣፈጡን የምንወስዳቸው ምግቦችና መጠጦች መዘዛቸው ከባድ በመሆኑም ጥንቃቄ ልንወስድ እንደሚገባ የስነምግብ ባለሙያዎች ያሳስባሉ፡፡     

Published in ዋናው ጤና
Saturday, 18 July 2015 11:33

ፀጉርዎ እየሳሳ ነው….?

   የፀጉር መሳሳት የበሽታ ምልክት ሊሆን ይችላል፡፡ የታይፎይድ እጢና የስኳር በሽታዎች የፀጉር መሳሳትን የሚያስከትሉ በሽታዎች ናቸው፡፡ ችግሩ ከመባባሱና አስከፊ ሁኔታ ላይ ከመድረስዎ በፊት ሃኪምዎን ያማክሩ፡፡
አመጋገብዎን ያስተካክሉ፡፡ የተስተካከለ አመጋገብ ጤናዎንና አካልዎን ብቻ ሳይሆን በፀጉርዎ ላይም የራሱን አሉታዊና አዎንታዊ ተፅዕኖዎች ማሳረፍ ይችላል፡፡ ስለዚህም ስለሚመገቡት ምግብ ምንነትና ጠቀሜታ አብዝተው ይጨነቁ፡፡
አዕምሮዎንም ሆነ ሰውነትዎን ያሳርፉ፡፡ ድካምና እረፍት ማጣት የፀጉር መመለጥን (መሳሳትን) ከሚያስከትሉ ምክንያቶች ዋንኞቹ ናቸው። ህይወትዎ ምንም ያህል በውጥረት የተሞላ እንኳን ቢሆን ለራስዎ ጊዜና እረፍት መስጠት ይኖርብዎታል፡፡  እንደ ዮጋና ሜዲቴሽን፣ ያሉ ነገሮች ጭንቀትና ውጥረትን ለማስወገድ እጅጉን ይረዳሉ፡፡ ለፀጉርዎ የሚጠቀሟቸውን ሻምፖና ኮንድሽነሮች እንዲሁም የሚቀቧቸውን ቀለማት ምንነትና አጠቃቀም በደንብ ይረዱ፡፡ በአግባቡ ያልተረዷቸውን ምርቶች ከመጠቀም ይቆጠቡ፡፡
በሻምፖ፣ በኮንድሽነሮችና በፀጉር ማቅለሚያዎች ውስጥ ያሉት ኬሚካሎች የፀጉር መሳሳትና መመለጥን ከሚያፋጥኑ ነገሮች መካከል በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ። ከእነዚህ ይልቅ ተፈጥሮአዊ ይዘታቸውን ያልለቀቁ ንጥረነገሮችን አዘውትረው ይጠቀሙ።

Published in ዋናው ጤና

  ወቅቱ ክረምት ነው፡፡ ልጆች የዓመቱ ትምህርታቸውን አጠናቀው እረፍት የሚያደርጉበት ጊዜ፡፡  በዚህ የክረምት ወቅት ልጆች እንደየአካባቢያቸው፣ እንደየቤታቸውና እንደየልማዳቸው የእረፍቱን ጊዜ የሚያሳልፉባቸው መዝናኛዎች አሏቸው፡፡
በአሁኑ ጊዜ እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች በስፋት እየተለመዱ ከመጡ የልጆች መዝናኛዎች መካከል ፊልሞች፣ ጌሞችና ፕሌይ ስቴሽኖች ይጠቀሳሉ፡፡
በተለይ የተለያዩ ጌሞችን ከኢንተርኔት በቀጥታ በመውሰድ ልጆች በስልኮች፣ በላፕቶፖችና በቲቪ ስክሪኖች ጭምር እንዲጫወቱበት ማድረግ እየተለመደ መጥቷል፡፡
ይሁን እንጂ እነዚህ ጌሞች ከመዝናኛነት ባለፈ ልጆችም ትምህርት የሚያገኙባቸው እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለልጆችዎ የሚመርጧቸው ጌሞች ቀለል ባለ መልኩ ህፃናት እየተዝናኑ እንዲማሩባቸው ሆነው የተዘጋጁ ሊሆኑ ይገባል። ለህፃናት በሚመች መልኩ የተሰሩና ህጸናትን እያዝናኑ ለመማር ያስችላሉ የሚባሉ ጌሞችን ከያዙ ድረ-ገፆች መካከል ጥቂቶቹን እነሆ፡-
Learning games for kids
በዚህ ዌብሳይት ላይ ያሉት ጌሞች በተለያዩ ዝርዝር ጉዳዮች የተከፋፈሉ ናቸው
Educational songs and videos
የህፃናት መዝሙሮችንና ሳይንስና ምርምር ነክ የሆኑ ነገሮችን ቀለል ባለ ሁኔታ የሚያስረዱና ዝግ ባለ እንቅስቃሴ የተዘጋጁ ቪዲዮዎች የሚገኙበት ክፍል ነው፡፡    
Health games
ልጆች ስለ አለርጂክ፣ ስለ ጥርስ ጤና አጠባበቅ፣ ስለ ጤናማ ሰውነት አቋም እንዲያውቁ የሚያግዙ መረጃዎችን በአዝናኝ መንገድ ያቀርባል፡፡  
Maths games
ልጆች በጨዋታ መልክ ስለ ሂሳብ ጠቃሚ ዕውቀቶችን የሚገበዩበትና የሂሳብ ችሎታቸውን የሚያሻሽሉበት ጌሞችን የያዘ ክፍል ነው፡፡
Geography games
ልጆች የተለያዩ የዓለም ክፍሎችን እንዲያውቁ የሚረዱ ጌሞች የተካተቱበት ነው፡፡
Science games
በእንስሳት፣ በተፈጥሮና፣ በህዋ ላይ ባሉ ሳይንሳዊ እውነታዎች ላይ ተመስርተው የተሰሩና ለልጆች መሠረታዊ ዕውቀትን የሚያስጨብጡ ጌሞች ያሉበት ነው፡፡
Keyboarding games
ልጆች በኮምፒዩተር የመፃፍ ችሎታቸውን እንዲሁም የቋንቋ ዕውቀታቸውን ለማዳበር የሚያስችላቸውና ጥሩ ክህሎትን የሚጨብጡበት ጌሞች የሚገኙበት ክፍል ነው፡፡
Miscellaneous games  
እኒህ ልጆችን እያዝናኑ የሚያስተምሩ ልዩ ልዩ ጨዋታዎችን ያካተቱ ጌሞች ናቸው፡፡
Pre-school games  
በአፀደ ህፃናት ደረጃ ላይ ያሉ ህፃናትን እያዝናኑ የሚያስተምሩ ጌሞች ይገኙባቸዋል፡፡
ወላጆች፡- ልጆቻችሁ አልባሌ ፊልሞችን እያዩ ጊዜያቸውን ከሚያጠፉ እንዲህ ዓይነት ጌሞችን በመጫን፣ የእረፍት ጊዜያቸውን የትምህርትና የመዝናናት ብታደርጉላቸው አይሻልም?! 

Published in ዋናው ጤና

አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ የኧርነስት ኤንድ ያንግ የኢትዮጵያ ማኔጂንግ ፓርትነርና ትራንሲሽን አድቫይሰሪ ሰርቪስ (TAS) ኃላፊ ናቸው፡፡ በ3ኛው ፋይናንስ ለልማት ዓለም አቀፍ ጉባኤ፣ የኢትዮጵያ ገበያ እየፈጠረ ያለውን አስገራሚ ዕድገትና የኢንቨስትመንት አማራጮች አስመልክተው ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ፤ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ የሚጋብዙ 10 ምርጥ ምክንያቶች በሚል ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ እኛም Investing in Emerging Ethiopia በሚል ርዕስ በጁላይ 2015 በታተመ መጽሔት የቀረቡትን 10 ምርጥ ምክንያቶች በዚህ መልኩ አቅርበናል፡-
1.የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፡- ኢትዮጵያ ከሰሐራ በታች ካሉ አገሮች ከደቡብ አፍሪካ፣ ከናይጀሪያና ከአንጐላ ቀጥላ አራተኛዋ ባለግዙፍ ኢኮኖሚ ናት፡፡ ኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ካላቸው የዓለም አገራት አንዷ ስትሆን እ.ኤአ በ2017 ከአፍሪካ ግዙፍ ኢኮኖሚ 3ኛ ለመሆን እየሠራች ነው፡፡ በ2013 የኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከ250 በመቶ በላይ የጨመረ ሲሆን አንድ ቢሊዮን ያህሉ ካደጉትና በማደግ ላይ ካሉ አገራት የመጣ ነው፡፡
ከፍተኞቹ ኢንቨስተሮች ቻይና፣ ሕንድ ሳዑዲ አረቢያ፣ ቱርክ፣ እንግሊዝና ኔዘርላንድስ ናቸው። በኤርነስት ኤንድ ያንግ ትንበያ መሠረት፤ የኢትዮጵያውያን የነፍስ ወከፍ ገቢ ከ2014 እስከ 2025 በየዓመቱ 18 በመቶ እያደገ መካከለኛ ገቢ ትደርሳለች ከተባለበት ጊዜ አንድ ዓመት ቀድማ በ2024 መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ትሰለፋለች፡፡ የኢትዮጵያን ዕድገት የሚጠቁሙ ሌሎች ነጥቦችም በዝርዝር ቀርበዋል፡፡
2. የሕዝብ ቁጥር ዕድገት፡- የኢትዮጵያ የሕዝብ ቁጥር ዕድገት ከፍተኛ ሲሆን ወጣቶችና መሰልጠን የሚችል ሕዝብ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር አማካይ ዕድሜ ከ20 ዓመት በታች ነው፡፡ ይህም ከፍተኛ የመሥራት አቅም ያላቸው የሰው ኃይል ማለት ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ2070 የናይጀሪያ ሕዝብ ቁጥር 639 ሚሊዮን ቢደርስም ኢትዮጵያ 225 ሚሊዮን ሕዝብ በመያዝ ከአፍሪካ ሁለተኛ እንደምትሆን ዋሽንግተን ፖስት ጁላይ 2013 ባወጣው ሪፖርት ተንብየዋል፡፡
የኢትዮጵያውያን አማካይ በሕይወት የመኖር ዕድሜ (Life expectancy) ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር ሲነፃፀር ትልቅ ነው፡፡ በ2012 የኢትዮጵያውያን በሕይወት የመኖር ዕድሜ 63 ዓመት ሲሆን፤ የኬንያ 61፣ የታንዛንያ 61፣ የደቡብ አፍሪካ 56፣ የናይጀሪያ 52፣ የአንጐላ 52 ዓመት ነበር፡፡
ኢትዮጵያ ያላት አየር መንገድ ከአፍሪካ አገሮች ትልቁና እጅግ አትራፊ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን የሚመራ ነው፡፡ የአፍሪካ አየር መንገዶች ትርፍ አንድ ላይ ቢደመር እንኳ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትርፍ በጣም ይበልጣቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ብዙ አውሮፕላኖች አሉት፡፡  ከአፍሪካ አየር መንገዶች ለ6 ተከታታይ ዓመት እጅግ ፈጣን ዕድገት ያሳየ ነው፡፡ በአፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች የኢትዮጵያ አየር መንገድ ድሪምላይነር 787 አውሮፕላን በማብረር ቀዳሚ ነው፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትርፍ በ2013 ዓ.ም 143 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን የደቡብ አፍሪካ 42 ሚሊዮን ዶላር፣ የኬንያ ኤርዌይስ 92 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡
3. ፈጣን የከተሞች ዕድገት፡- ከተሞች የዓለም የዕድገት ኃይል ምንጭ ናቸው፡፡ በ2030 ከዓለም 50 ምርጥ ከተሞች ውስጥ ግማሾቹ ፈጣን ዕድገት ካላቸው አገሮች ናቸው፡፡ አዲስ አበባ በ2025 ዓ.ም 6.1 ሚሊዮን ሕዝብ በመያዝ፣ ብዙ ሕዝብ ከሚኖራቸው ከተሞች 5ኛ እንደምትሆን ተተንብዮአል፡፡
የአዲስ አበባ ቀላል የባቡር ትራንስፖርት ከሰሐራ በታች ካሉ አገሮች የመጀመሪያው ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በኢኮኖሚ ዕቅዱ ውስጥ ለከተማ ማዕከላት ዕድገት ቅድሚያ ሰጥቷል፡፡ ትላልቅ የከተማ ሰፈሮች መፈጠር ኢንቨስትመንት ከመሳቡም በላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን ይጨምራል፡፡ ከ300ሺህ ሕዝብ በላይ  የሚኖርባቸው የኢትዮጵያ ከተሞች በ2030 በጣም ብዙ እንደሚሆኑ ተገምቷል፡፡
4. የአፍሪካ የማኑፋክቸሪንግ ማዕከል፡- አሁን ባለው ሁኔታ፣ ኢትዮጵያ በ2025 ከአህጉሩ ቀዳሚ የማኑፋክቸሪንግ ማዕከሎች ከደቡብ አፍሪካ፣ ከናይጀሪያና ከኬንያ ቀጥላ እንደምትሆን የኧርነስት ኤንድ ያንግ ጥናትና ትንታኔ እንዲሁም ከተለያዩ የውጭ ምንጮች የተገኙ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ እሴት በሚጨመርባቸው ጉልበት በሚፈልጉ ቀላል የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች፣ በሸቀጣሸቀጦች፣ በጨርቃጨርቅ፣ በቆዳ፣ በኮንስትራክሽን ማቴሪያልስ፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ እሴት በሚጨመርባቸው ጥሬ ዕቃዎች… የአህጉሩ ምርጥ የማኑፋክቸሪንግ ማዕከል ለመሆን እየሠራች ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለተወዳዳሪነት ከፍተኛ ዋጋ ባለው የማኑፋክቸሪንግ የጉልበት ዋጋ ከዓለም ዝቅተኛው ክፍያ የሚፈፀምባት አገር ናት፡፡ የአሜሪካ ዓለምአቀፍ የሠራተኞች ስታቲስቲክስ በ2013 ባወጣው ሪፖርት፤ በኢትዮጵያ ለአንድ የማኑፋክቸሪንግ ሠራተኛ በሰዓት የሚከፈለው 0.41 የአሜሪካ ሳንቲም ነው፡፡ ማኑፋክቸሮች ተወዳዳሪ የሚሆኑበት አንዱ መንገድ የኤሌክትሪክ ዋጋ ዝቅተኛነት ነው፡፡ በዚህ ረገድ በዓለም የኤሌክትሪክ ዋጋ ክፍያ ርካሽ የሆነባት አገር ኢትዮጵያ ነች፡፡
5. መሠረት ልማት፡- በኢትዮጵያ የመሠረተ ልማት ግንባታ በከፍተኛ ደረጃ እየተጧጧፈ ነው፡፡ ኧርነስት ኤንድ ያንግ ከ2010 እስከ 2025 በመንገድ፣ በባቡር፣ በቴልኮም፣ በኃይል፣ በውሃ፣  የአውሮፕላን ግዢን ጨምሮ ከ101 ቢሊዮን በላይ በመሠረተ ልማት ዘርፍ ወጪ እንደሚደረግ ገምቷል፡፡ የኢንዱስትሪ ዞኖች ግንባታ ማኑፋክቸሪንግን ለማሳደግ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ በሰሜን አዲስ አበባ 5 የኢንዱስትሪ ዞኖች ለናሙና የሚገነቡ ሲሆን በመላው አገሪቱ ደግሞ 15 ዞኖች ይሠራሉ፡፡ በዚህ ዓመት በአዲስ አበባ ለሚገነባው ሁለተኛው የኢንዱስትሪ ዞን ግንባታ የዓለም ባንክ 250 ሚሊዮን ዶላር ብድር ፈቅዷል፡፡
ኢትዮጵያ በ2023 ሁለተኛዋ ትልቅ የኤሌክትሪክ ኃይል ኤክስፖርተር በመሆን ከቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ እንደምታገኝ እንዲሁም በአፍሪካ ከናይጄሪያና ደቡብ አፍሪካ ቀጥላ 3ኛዋ ትልቅ የቴሌኮም ገበያ እንደምትሆንና 5ሺህ ኪ.ሜትር የኤሌክትሪክ ባቡር አዲስ እንደምትገነባ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአፍሪካ ትልቁ የዕቃ መጫኛ ካርጎ እንዳለው ተገልጿል፡፡
6. ግዙፍ የተፈጥሮ ሀብት፡- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ የዘይት፣ ጋዝና የማዕድን ቁፋሮ ተጀምሯል፡፡ የቻይናው ኩባንያ፣ ከካሉብና ከሂላላ የጋዝ ጉድጓዶች ጋዝ ወደ ኤስያ አገሮች ለመላክ ከኢትዮጵያ ወደ ጅቡቲ ወደብ የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ እየዘረጋ ነው፡፡ የሩሲያ፣ የአሜሪካ፣ የእንግሊዝ… የማዕድን አሰሳና ፍለጋ ለማካሄድ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
ኢትዮጵያ በማዕድን ዘርፍ ፕላቲኒየም ታንታለም፣ ብረትና የፖታሽ ማዕድን አላት፡፡ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ብቸኛዋ ኦፓል አምራች አገር ናት፡፡
7. እርሻ፡- ኢትዮጵያ ትልቅና ያልተነካ እምቅ የእርሻ ሀብት ባለቤት ናት፡፡ ኢትዮጵያ 74 ሚሊዮን ሄክታር ያልታረሰና 15 ሚሊዮን ሄክታር የታረሰ የእርሻ መሬት አላት፡፡ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ትልቋ የስንዴ አምራች ስትሆን በዓለም ትልቋ የጤፍ አምራች ናት፡፡ ጤፍ በካልሲየም ብረትና ፕሮቲን የበለፀገ ሲሆን አለርጂ ከሚያስከትለው ጉለቲን ማልያ ነፃ ነው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ለመካከለኛ ምስራቅ ለአውሮፓ፣ ለኤስያና ከዚያ ወዲያ ላሉ አገሮች ኤክስፖርት ለማድረግ አመቺ ናት፡፡ ኢትዮጵያ በቡና ምርት ኤክስፖርት ከብራዚል፣ ቪየትናም፣ ኢንዶኔዥያና ኮሎምቢያ ቀጥላ 5ኛ ናት፡፡ ስታር ባክስ የኢትዮጵያን ቡና ገምግሞ ከ5 ነጥብ 4.8 ሰጥቷል፡፡ ኢትዮጵያ የወይን አምራችና ላኪ አገርም ሆናለች፡፡
8. ቱሪዝም፡- ስለኢትዮጵያ የቱሪስት መስህቦች ሲኤንኤን ስለሰሜን ተራራ “ከመሞትህ በፊት ማየት ያለብህ ስፍራ” (Place to see before you die) በማለት ገልጿል፡፡ ሁፍንግ ፖስት የተባለው ደግሞ ስለ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ሲገልጽ፤ “መታየት ያለባት ከተማ” (City to Visit) ብሏታል። “Over looked and under - visited, Ethiopia is Africa’s best kept secret” - 1000 place to see before you die ተብሏል፡፡
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ በርካታ በዩኔስኮ የተመዘገቡ የቱሪስት መስህቦች ያላት አገር ናት፡፡ ኒውዮርክ ታይምስ በ2014 ባወጣው ሪፖርት፤ በዓለም ከተጎበኙ አገሮች ኢትዮጵያን ከምርጥ 52 የዓለም የቱሪስት መዳረሻዎች በ13ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል፡፡
9. በቢዝነስ አመቺነት፡- የዓለም ባንክ በ2014 ባወጠው ሪፖርት መሰረት፤ ኢትዮጵያ፣ ከአፍሪካ አገሮች በቢዝነስ ምቹነት ከደቡብ አፍሪካና ከጋና ቀጥላ 3ኛ ናት፡፡
10. የስትራቴጂ አቀማመጥና ነፃ ገበያ፡- ኢትዮጵያ ለ3.5 ቢሊዮን ሰዎች ቅርብ የገበያ መዳረሻ ስትሆን በ8 ሰዓት ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ ከጂዳ 2፡45፣ ከዱባይ 3፡35፣ ከአቡጃ 4፡40፣ ከጆሃንስበርግ 5፡30፣ ከኢስታንቡል 5፡25፣ ከዴልሂ 6፡40፣ ከፍራንክፈርት 7፡20 ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡   

     ከሁለት ሳምንት በፈት በዓለም ትልቅ ስም ያላቸው ታዋቂ ሆቴሎች ወደ አፍሪካ እየተመሙ መሆናቸውን ነግረናችሁ ነበር - መዳረሻቸውን ሳንጠቅስ፡፡ አሁን ከመዳረሻ አገሮች አንዷ ሩዋንዳ መሆኗ ታውቋል፡፡
በሩዋንዳ በሆቴል ዘርፍ ኢንቨስት ለማድረግ ከቆረጡት ታዋቂ ሆቴሎች መካከል ማሪዮት፣ ራዲሰን ብሉ፣ ሸራተን፣. ጎልደን ቱሊፕ፣ ራድሰን ባይ ፓረክ ኢን፣ ኮፒሶንኪና ዚንክ ጥቂቱ መሆናቸውን ቤንች ኢቨንት አስታውቋል፡፡
በዓለም ታዋቂ የሆኑ የበርሊን፣ የዱባይ፣ የስታቡልና የሞስኮን የሆቴል ኮንፈረንሶች በማዘጋጀት የሚታወቀው ቤንች ማርክ ባለፈው ሳምንት ባሰራጨው ዜና፤ ሩዋንዳ በ2016 የአፍሪካን ሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረምን እንደምታዘጋጅ ገልጿል፡፡ ከዚያ በፊት በ2015 የሚደረገው ተመሳሳይ ኮንፈረንስ ከሴፕቴምር 30 እስከ ኦክቶበር 1 በአዲስ አበባ በሸራተን ሆቴል ይካሄዳል ተብሏል፡፡
የሩዋንዳ መንግስት ይህን የዓለም ሆቴሎች ኮንፈረንስ ፎረም የሚያዘጋጀው በአገሪቷ የቱሪዝም ልማት ቦርድ አማካይነት ነው፡፡ የአፍሪካ ሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረም (ኤ.ኤች አይ ኤፍ) በዓለም ታዋቂ የሆኑ የሆቴል ኢንቨስተሮችን ከአገሬው የዘርፉ ተዋናዮች፣ ከሚኒስትሮች፣ ከመንግስት ባለሥልጣናትና የሆቴል ኢንዱስትሪ ኤክስፐርቶች ጋር በማገናኘት ለዘርፉ ዕድገት የሚሰራ ፎረም ነው። ኤኤች አይ ኤፍ ኮንፈረንሱን በኪጋሊ - ሩዋንዳ ለማካሄድ የወሰነው የሩዋንዳ መንግሥት በቱሪዝም ዘርፍ ኢንቨስትምንትን ወደ አገሩ ለመሳብ በቀረጸው ስትራቴጂ እንደሆነ ቤንች ማርክ ገልጿል፡፡
አምባሳደር ያሚና ካታሪኒዲ በሩዋንዳ የልማት ቦርድ የቱሪዝም ዋና ኃላፊ ሲሆኑ የኤ ኤች አይ ኤፍ ለማዘጋጀት የወሰኑት በአፍሪካ የሆስፒታሊቲ ኢንዱስትሪ በሆነው የቱሪዝም ዘርፍ ኢንቨስት ማድረግ በዓለም እጅግ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑትን አብዛኞቹን ኢንቨስተሮችና ውሳኔ ሰጪዎች ለማግኘት ስለሚረዳ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ “ግንኙነት ለመፍጠርና ሩዋንዳ፣ ቢዝነስ ለማካሄድ ትክክለኛ ስፍራ መሆኗን ለማመልከት ወስነናል። ስለዚህ ኮንፈረንሱን ማዘጋጀት የአገር ውስጥ ኢንቨስተሮች ከውጪ ከሚመጡት ጋር ለመገናኘት ዕድል ይፈጥርላቸዋል” ብለዋል፡፡
የዓለም የጉዞና ቱሪዝም ካውንስል በመላው አፍሪካ ጉዞና ቱሪዝም ከፍተኛ የዕድገት መስህብ እንዳለው ጠቅሶ፣ በአፍሪካ አገራት ጂዲፒ 8.1 በመቶ ድርሻ እንዳለውና እስከ 2025 በየዓመቱ እስከ 4.9 በመቶ እንደሚያድግ መተንበዩን አስታውቋል፡፡
የሩዋንዳ የቱሪዝም ዕድገት ዋነኛ ምንጯ መዝናኛዎቿ ናቸው፡፡ በመሆኑም በአሁኑ ወቅት አገሪቷ የስብሰባና የቱሪዝም ኤግዚቢሽን ማዕከል፣ በአገሪቷ የፀጥታ ደህንነትና በመሰረተ ልማት አዳዲስ ወደዘርፉ የሚገቡትን አዳዲስ ሆቴሎች ለማጥመድ እየሰራች መሆኗን ገልፃለች፡፡
የሩዋንዳ የቱሪዝም ዘርፍ በዕድገት ጎዳና ግስጋሴውን ቀጥሎ በ2013 እና በ2014 በአገሪቷ ቀዳሚውን ስፍራ ይዟል፡፡ ሩዋንዳን የሚጎበኙ ቱሪስቶች ቁጥር በየዓመቱ በ3 በመቶ እያደገ ሲሆን የቱሪስቶቹ ቁጥር ከ1.4 ሚሊዮን ወደ 1.2 ቢሊዮን ያደገ ሲሆን በገቢም ረገድ ዕድገት አሳይቷል፡፡ የ2013 ገቢ 293.4 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን የ2014 ደግሞ 303 ሚሊዮን ዶላር ሆኗል፡፡
በ2014 የአፍሪካ ሆቴል ኢንቨስትመንት የተካሄደው በአዲስ አበባ ሲሆን ከ40 ከሚበልጡ አገሮች፣ ከ500 በላይ ተሳታፊዎች፣ ከ400 የሚበልጡ ድርጅቶችን በመወከል ተገኝተው ነበር።

      በእስልምና ውስጥ በከፍተኛ ድምቀት የሚከበሩ ሁለት ኢዶች (በአሎች) አሉ፡፡ የመጀመሪያው የረመዳን ፆምን ማብቃት የሚያበስረው ኢድ - አልፈጥር ሲሆን፣ ሁለተኛው ደሞ ከሁለት ወራት በኋላ የሐጂ ስነ - ስርዓትን ተከትሎ የሚመጣው ኢድ - አልአድሓ (የእርድ በዓል ነው፡፡ ረመዳን ተጠናቆ የምናከብረው በዓል ኢድ አልፈጥር) ስለሆነ እኔም የማወራችሁ ስለዚሁ ክብረበዓል አጠቃላይ ገፅታ ነው፡፡
ረመዳን፤ ሙስሊም ምእመናን ራሳቸውን የሚያንፁበት፣ ወደ አምላክ የሚቀርቡበት የኢማን እውቀታቸውን የሚያሳድጉበት ልዩ የፆም ወር ነው። የረመዳን ወር ከሌሎቹ ወራቶች የተለየና  ትልቅ የሚያደርገው፣ ምእመናን ፀሐይ ከመውጣቷ በፊት አንስቶ እስከ ጠለቀችበት  ድረስ ከምግብ፣ ከውሐ፣ ከወሲብ ግንኙነት (ህጋዊ ትዳርን ጨምሮ)፣ ከመጥፎ ንግግር እና ባህሪ የተቆጠቡ መሆን ስላለባቸው ነው፡፡ በእርግጥ ህጋዊ ያልሆነ ወሲብን ጨምሮ ሌሎቹ መጥፎ ባህሪያት በሌላው ወር ይፈቀዳል ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን የወሩን ታላቅነት አፅንኦት ለመስጠት አላህ የደነገጋቸው ህጎቹ ናቸው። በተጨማሪም 30 ጁዝ (ምዕራፍ) የያዘውን ቅዱስ ቁርአንን ምዕመናን በረመዳን አንብበው የሚያጠናቅቁበት ወር ነው፡፡
የረመዳንን ወር ከአንድ አነስተኛ የማሰልጠኛ ተቋም ጋር ማመሳሰል እንችላለን፡፡ በአንድ ማሰልጠኛ ተቋም ውስጥ የሆነ ዘርፍ አጥንተን እውቀትና ስነ - ምግባሮች እንደምንጨብጠው ሁሉ፤ በረመዳን ወቅትም በቁርአን እውቀት አዕምሯችንን አበልፅገን፣ በመንፈሳዊ እሴቶች ተሐድሶ ወስደን የምንወጣበት ወር ነው፡፡ ወይም ደግሞ በአንድ ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ ሰልጣኞች አካላቸውን ለማፈርጠም እና የሰውነታቸውን ጥንካሬ ለማረጋገጥ የተለያዩ ስልጠናዎችን እንደሚወስዱት ሁሉ፤ በረመዳንም ምእመናን መንፈሳዊ ጥንካሬን ለማግኘት እምነቱ የሚያዘውን አመጋገብ ዘይቤ ይለውጣሉ፡፡ እንዲሁም በረመዳን ወር ብቻ የሚገኙ ሃይማኖታዊ ስልጠናዎችን ተግብረው ቀሪውን ህይወታቸውን ከፈጣሪ ጋር ለማቀራረብ ይሞክራሉ፡፡ በጎ ስራዎችን ማሳደግ እና የአምልኮ ስርአቶችን በብዙ መፈፀም ሌሎቹ የስልጠና ግብአቶች ናቸው፡፡
ራሳችንን ከምግብና ከውሃ ማቀብ፣ በድህነት ለሚኖሩ ሚስኪኖች እንድናስብ ያደርገናል፡፡ ምግብና ውሃ አጥቶ መኖር ምን እንደሚመስል የምናውቀው በረመዳን ወር ነው፡፡ ምግብና ውሃ ብቻ ሳይሆን ሌሎች የቅንጦት ነገሮችን ማጣት ያለውን ስሜት በረመዳን ወር ፍንትው ብሎ ይታየናል፡፡ ራስን ዝቅ አደርጎ ለፈጣሪ መስገድ ያለውን እርካታ ረመዳን ይነግረናል፡፡ ማፍጠሪያ ሰዓት ደርሶ ከቤተሰብ እና ከወዳጆች ጋር ተሰብስቦ አብሮ መብላት ራሱን የቻለ የማህበራዊ በጎ እሴት ነው፡፡ ከነዚህ ስልጠናዎች በኋላ የሚቀረን ተመርቆ ከስልጠናው መሰናበት ነው፡፡ የረመዳን ምረቃ ደግሞ ኢድ - አልፈጥር ነው። ምእመናን ኢድ - አልፈጥርን በማክበር ከረመዳን ስልጠናዎች ተመርቀው ይወጣሉ፡፡
ኢድ - አልፈጥር ትርጉሙ ራሱ የፆም ማጠናቀቂያ ክብረ - በአል እንደማለት ነው፡፡ በአብዛኛው “የአለም ሀገሮች ውስጥ ለ3 ቀናት በድምቀት ይከበራል፡፡
ኢድ አልፈጥር በብዙ ሀገሮች በተለያዩ መንገዶች ቢከበርም የጋራ የሆነ አንድ ነገርን ይዟል፡፡ ይሄውም በበአሉ ቀን ሁሉም አማኞች በጧት ተነስተው ልዩ የሶላት ስግደት ወደሚደረግበት ቦታ ይተማሉ። በኛ ሀገር ምእመናን በለሊት 11 ሰዓት ተነስተው ወደ ስግደት ከመሄዳቸው  በፊት ተሰብስበው ገንፎ በቅቤ ወይም በተልባ ይበላሉ፡፡ አሁን አሁን ብዙም ባይስተዋልም እንጀራ በፌጦ የመጉረስ ልማድ ነበር። (በሀገራችን ለዘመን መለወጫ መስከረም ላይ እንደሚደረገው አይነት)
የኢድ-አልፈጥር ስግደት የሚደረገው በመስጂድ ውስጥ ወይም ሁሉንም አማኝ ሊያሰባስብ በሚችል አንድ ገላጣ ቦታ ላይ ነው፡፡ የእምነቱ ተከታዮች በቡድን እየሆኑ ተክቢራ በማድረግ (የበአሉ የውዳሴ ዜማዎች) ወደ ስግደቱ ቦታ ይተማሉ፡፡ በሀገራችን ውስጥ ሙስሊሞች ከተለያዩ አቅጣጫዎች በቡድን እየሆኑ፣ ተክቢራ እያደረጉ ወደ ስታዲየም እንደሚሄዱት ማለት ነው፡፡
ከስግደት መልስ ምእመናን የበአል ድግስ አድርገው ከቤተሰብ፣ ከዘመድ - አዝማድ እንዲሁም ከጐረቤት ጋር በአሉን በደስታ ያሳልፋሉ፡፡ ቤተ ዘመዶችን እየዞሩ መጠየቅና እንኳን አደረሳችሁ ማለት የኢድ አልፈጥር ልዩ ባህሪው ነው፡፡ የምግቡ አይነት እንደየባህሉ ከሀገር ሐገር ቢለያይም፣ ልዩ ምግቦችን ማዘጋጀት ግን የማይቀር ጉዳይ ነው። በተለይ ህፃናቶች በኢድ አልፈጥር ጊዜ በአዲስ ልብሶች አጊጠው በዘመድ አዝማድ ቤቶች እየዞሩ “የሚናኢድ” በማለት ሳንቲሞችን ይቀበላሉ፡፡ ይህ በአል በህፃናቶች ዘንድ ልዩ በመሆኑ ከቤተሰብና ከዘመድ አዝማድ የሚሰበሰቡት ሳንቲሞች በጣም ብዙ ናቸው፡፡
አንድ ሙስሊም በረመዳን ማፍጠሪያ ወቅት ምጽዋት ያልሰጠ ከሆነ የኢድ አልፈጥርን በአል ተጠቅሞ ለሚስኪኖች ዞካ መስጠት አለበት፡፡ የምግብ አልያም የገንዘብ ስጦታ ሊሆን ይችላል፡፡ ብዙ ሙስሊሞች የበአል ድግስ አድርገው ደሐዎችን ያበላሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ የታረዙትን ያለብሳሉ፡፡ ምንም ይሁን ነገር ግን በኢድ አልፈጥር በአል ወቅት ለድሐዎች የምጽዋት እጆችን መዘርጋት ሐይማኖቱ የሚመክረው በጐ ተግባር ነው፡፡ መልካም የኢድ አልፈጥር በአል ለመላው የእስልምና ተከታዮች በሙሉ እንዲሆን እየተመኘሁ እሰናበታለሁ፡፡  

Published in ህብረተሰብ

• ኒዮሊበራሎች ቀላል ሲያደንቁን ሰነበቱ…
• ለኢትዮጵያ ህፃናት ዲሞክራሲ በጡጦ ይሰጣቸው!
• የዲሞክራሲ ነገር ለዛሬው ትውልድ ዘገየ (too late!)

   እናንተዬ …ለካስ      ኒዮሊበራሎችን   አናውቃቸውም። ሰይጣን ነበር እኮ የምናስመስላቸው። (የቀለም አብዮት ጠንሳሽ ምናምን እያልን!) …ኢህአዴግንማ ተውት! ከተቃዋሚ ፓርቲዎች እንደ አንዱ ነበር የሚቆጥራቸው፡፡ (የሚያወርድባቸው ስድብ ትዝ አላችሁ!) አንዳንዴማ… በአስቸጋሪ የአማርኛ ተረቶች አጅቦ የሚያዥጐደጉድባቸው ነገር በእንግሊዝኛ ለመተርጐምም ሳያስቸግር አይቀርም (ለብልሃቱ ይሆን እንዴ?!) የሆኖ ሆኖ ግን ሰሞኑን እንዳየናቸው እነሱ ቂም አልያዙም፡፡ (እኔም ኒዮሊበራል ሆኛለሁ!)
እናላችሁ…በ3ኛው ዓለምአቀፍ የፋይናንስ ጉባኤ ለልማት ላይ ብዙዎቹ የኒዮሊበራል አቀንቃኞች በሚያስገርም ሁኔታ የጦቢያን የዕድገት ለውጥ እያደነቁ Congra… Celebration…ምናምን ዓይነት ውደሳዎች… ሲያዘንቡብን ነው የሰነበቱት። በእርግጥ በደረቁ ቢሆን ኖሮ ትንሽ ያሰለቸን ነበር (የኢህአዴግን አላውቅም!) ደግነቱ ግን ገንዘባቸውን እያወጡ  ነው ያደነቁን፡፡ (መታደል እኮ ነው!) ለሆቴል አልጋ… ለምግብና መጠጣቸው… ምሽት ላይ ሲዝናኑ… የመኪና ኪራይ… ከመዲናዋ ወጣ ብለው የቱሪዝም መስህቦችን ሲጐበኙ… ቀላል ይከፍላሉ (ጨዋታው እኮ በዶላር ነው!) በነገራችን ላይ በኮንፍረንስ ቱሪዝም ዙሪያ በEBC ማብራሪያ ሲሰጡ የሰማኋቸው ተርብ ተናጋሪ፤ በሰሞኑ ጉባኤ ጦቢያ በትንሹ እስከ 20 ሚ.ዶላር ገቢ ማግኘቷን ገምተዋል፡፡ ግማሹ ራሱ እኮ ቀልድ አይደለም (ያውም በጠፋ ምንዛሪ!) እኚሁ ባለሙያ (ካድሬማ ፕሮፓጋንዳ እንጂ ኢኮኖሚ አያውቅም!) የጉባኤ ቱሪዝም ላይ አተኩረን ከሰራን - የውጭ ምንዛሪ ገቢያችንን በቀላሉ ማሳደግ እንደምንችል ተናግረዋል። (ነቄ ባለሙያ ብያለሁ!) ይታያችሁ… በ5 ቀናት ከ5ሺ በላይ የጉባኤ ተሳታፊዎችን “ቤት ለእንግዳ” ብቻ ስላልን 20 ሚ. ዶላር (400 ሚ. ብር ገደማ እኮ ነው!) ከዘጋን ምን እንፈልጋለን? (መንግስት የአንድ ወር ታክስ ይማረን!) በቀጣዩ ሳምንት ደሞ ኦባማ አሉልን፣ (ጊዜው የኛ እኮ  ነው!) በነሐሴ እንዲሁ በዳያስፖራ እንጥለቀለቃለን (ብቻ እንደ ሚሊኒየሙ ጉድ እንዳይሰሩን!) እናላችሁ… ያኔ ኢህአዴግ ባለ 2 ዲጂት ዕድገት ምናምን የሚለውም ነገር በደንብ ይገባናል፡፡ (ካጣጣምነው አዎ!)
እናላችሁ… አንዳንድ አገራት ኒዮሊበራል ቢሆኑም በዕድገታችን ሲደመሙ እንጂ ዓይናቸው ደም ሲለብስ ስላላየን… ኢህአዴግ ፍረጃውንና ታፔላ መለጠፉን ቀነስ ቢያደርግ ክፋት የለውም (ትዝብት እኮ ነው ትርፉ!)
እኔ የምላችሁ… ለዳያስፖራው ጉባኤ በEBC የሚደረገው ያልተለመደ በትህትና የተጠቀለለ ግብዣ… የኦባማን የኢትዮጵያ ጉብኝት በመቃወም ዋይት ሃውስ ደጃፍ ላይ ሰልፍ የወጡትንም ይጨምራል… ወይስ እንዴት ነው? (“አውቀው በድፍረት ሳያውቁ በስህተት” በሚል ታልፈው ከሆነ ብዬ እኮ ነው!) አንድ ነገር ግን ሁሌም ግርም ይለኛል፡፡ የአበሻ ልጅ በየቀኑ እንደ ጉድ ይሰደዳል፡፡ (በፖለቲካውም በኢኮኖሚውም እያኮረፈ!) ከዚያስ? የዳያስፖራ ጥሪ እንደጉድ ይዥጐደጐዳል፡፡ (በፀባይ ሆነ እንጂ “ሰዶ ማሳደድ እኮ ነው!”) መጀመሪያውኑ ተስማምቶ መኖር የአባት ነው፡፡  እንዴት ነው ግን በጦቢያ ምድር እንዲህ ኩርፊያ የነገሰው? (የዚያ ትውልድ ውርስ እንበለው?!)
ይኼውላችሁ… እኛ እንደሆን ዲሞክራሲ ኮከባችን አይደለም፡፡ ቢያንስ ግን ለህፃናቱ  የዲሞክራሲ ት/ቤቶች ማሰልጠኛዎች በየአካባቢው ቢከፈቱ ሸጋ ይመስለኛል፡፡ ከእኛ ተመክሮ ተምረን ህፃናቱን በማለዳ በዲሞክራሲ ጠበል ማስጠመቅ የእኛ ዕጣፈንታ እንዳይገጥማቸው ያግዛቸዋል። አያችሁ… የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር  ወይም የመንግስት ባለሥልጣን ከሆኑ በኋላ ከዲሞክራሲ ጋር ለመለማመድ መድከም ትርፉ ጊዜ ማባከን ብቻ ነው (በሩብ ክ/ዘመን እኮ የመጣ ለውጥ የለም!) እንደውም የኋሊት ጉዞ እንጂ፡፡ ኢህአዴግን ወይም ተቃዋሚን “አምባገነን” በሚል ለማውገዝ አይደለም፡፡ ሃቅ ስለሆነ ብቻ ነው፡፡ ኢህአዴግም ሆነ ተቃዋሚዎች ሲፈጥራቸው ፀረ - ዲሞክራሲያዊ ሆነው እኮ አይደለም፡፡ ይልቁንም ስለማያውቁት ነው ወይም ስለማናውቀው፡፡
ከምሬ እኮ ነው… ዲሞክራሲ ባህላችን አይደለም። ከልጅነት እስከ ዕውቀት ትውውቅ የለንም፡፡ ባል ሚስቱን፣ አባት ልጁን፣ ተማሪ አስተማሪውን፣ አለቃ ሎሌውን፣ የቤት እመቤት የቤት ሠራተኛዋን… እንዴት ነው treat የሚያደርጉት?? (አሁንም ድረስ ባል ሚስቱን የሚቀጠቅጥበት አገር ውስጥ እኮ ነን!) እናላችሁ…እኛና ዲሞክራሲ ሩቅ ለሩቅ ነን፡፡ በቅርባችን የምናገኘው የሱን ተቃራኒ ነው፡፡ ዕድሜ ለደርግ! ጭቆናና አፈና ብርቃችን አይደለም! (ኖረነዋላ!) ነፃነትንና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ግን አናውቃቸውም ወይም ዋጋ አንሰጣቸውም። (መክሊታችን አይደለም!!) እንደ ትምህርት ቶሎ ቶሎ በማጥናት የሚደረስበት ደሞ አይደለም፡፡ (ስንቱ ምሁርና ሊቅ ዲሞክራት ይሆን ነበር!) ሌላው ቀርቶ ዲሞክራሲ የሰፈነበት አገር (የዲሞክራሲ ባህር ውስጥ እንደማለት!) በመቀመጥም የሚዋሃድ ነገር አይመስለኝም፡፡ (ዳያስፖራውን አታዩትም?!)
እኔ እንደተረዳሁት… ዲሞክራሲ እንደ እነ አይፎን User friendly (ለአጠቃቀም ምቹ!) አይደለም፡፡ (ለአሁኑ ትውልድ ማለቴ ነው!) ቶሎ የሚለመድም የሚላመድም አልመሰለኝም (ስንት ዓመታችን?!) ፌስቡክ ላይ አንዱ የግል ሃሳቡን በማንፀባረቁ ወይም አቋሙን በመግለፁ የሚወርድበትን ውርጅብኝ እናውቀው የለ! እናላችሁ… ዲሞክራሲን ለምደን ላንለምደው ከምንታገልና ጊዜያችንን በከንቱ ከምናባክን… ለህፃናቱ መሰረት ብንጥልላቸው ትልቅ የአገር ውለታ ነው፡፡ (ለኛማ ዲሞክራሲ… It is too late!) መፍትሔው ለህፃናቱ የዲሞክራሲ ተማሪ ቤቶችን ማስፋፋት ነው (ዲሞክራሲ በጡጦ ሊሰጣቸው ይገባል!)
እንደኛ ወተት ተግተው ብቻ ወደ ቀይ ወጥ ከተሻገሩ፣ እኛኑ ነው የሚሆኑት (ይሄኔ ነው ፈረንጅ disaster የሚለው!) እውነቱን ልንገራችሁ አይደል… ከዲሞክራሲ ባህል የተፋታ ትውልድ ማለት የባከነ ነው፡፡ ለራሱም ለአገሩም የማይበጅ! ለሁሉ ነገር ጉልበት የሚቀናው! የአያቱን ጭስ የጠገበ ጦር ከተሰቀለበት ለማውረድ የሚጣደፍ! (በራሱ ዘመን የማይኖር!) እናም የእኛን ነገር እርሱት! (It is too late for democracy!) ይልቅስ የወደፊት አገር ተረካቢ ህፃናትን  ከደማቸው ጋር ዲሞክራሲን ለማዋሃድ እንትጋላቸው፡፡ እንደኛ ሲጐለምሱ የደሙ ዓይነት (A) ከዲሞክራሲ (O) ጋር አልጣጣም ይልባቸዋል - (ደሙ አላውቅህም ይለዋል - ዲሞክራሲን!)
እናላችሁ...የአገራችን ህዝብ ሳይማር እንዳስተማርን ሁሉ እኛም ዲሞክራት ሳንሆን ልጆቻችንን ዲሞክራት እናድርጋቸው! (ዲሞክራት ሳይሆኑ ዲሞክራት ያደረጉን ብለው ያመሰግኑናል!) ሌላ ምርጫ አለኝ ብትሉኝም አልሰማችሁም፡፡ (ዲሞክራሲ ኮከቤ አይደለም!!)

Saturday, 18 July 2015 11:23

የፀሐፍት ጥግ

(ስለ ንባብ)
- ግሩም መፅሐፍ መጨረሻ የለውም፡፡
አር.ዲ. ከሚንግ
- ባህልን ለማጥፋት መፃህፍትን ማቃጠል
አያስፈልግም፡፡ ሰዎች ማንበብ እንዲያቆሙ ብቻ
ማድረግ በቂ ነው፡፡
ሬይ ብራድበሪ
- መፅሃፍ በእጅህ የምትይዘው ህልም ነው፡፡
ኔይል ጌይማን
- ሁሉም ሰው የሚያነባቸውን መፃህፍት ብቻ
የምታነብ ከሆነ፣ ሁሉም ሰው ከሚያስበው
ውጭ አታስብም፡፡
ሃሩኪ ሙራካሚ
- ራስህ የማታነበውን መፅሃፍ ለልጅ አለመስጠትን
መመሪያህ አድርገው፡፡
ጆርጅ በርናርድ ሾው
- በመፃህፍት ካልተከበብኩ በቀር እንቅልፍ
መተኛት አልችልም፡፡
ጆርጅ ሉዊስ ቦርጅስ
- መፅሃፍ ምናብን የሚያቀጣጥል መሳሪያ ነው፡፡
አላን ቤኔት
- የሰው ማንነት በሚያነባቸው መፃህፍት
ይታወቃል፡፡
ራልፍ ዋልዶ ኤመርሰን
- መፅሃፍ ስታነቡ ፈፅሞ ብቻችሁን አይደላችሁም።
ሱሳን ዊግስ
- ጥቂት ገንዘብ ሳገኝ መፃህፍት እገዛበታለሁ፡፡
ከዚያ ከተረፈኝ ምግብና አልባሳት እሸምታለሁ፡፡
ኢራስመስ
- እንደ መፅሃፍ ያለ ታማኝ ጓደኛ የለም፡፡
ኧርነስት ሄሚንግዌይ
- የምናነበው ብቻችንን አለመሆናችንን ለማወቅ
ነው፡፡
ሲ.ኤስ.ሌዊስ
- አሮጌውን ኮት ልበስና አዲሱን መፅሃፍ ግዛ፡፡
ኦዩስቲን ፉልፕስ
- ብዙ አንብቦ ትንሽ ከማሰብ፣ ትንሽ አንብቦ ብዙ
ማሰብ ይሻላል፡፡
ዴኒስ ፓርስንስ ቡርኪት
- ህፃናት አንባቢያን የሚሆኑት በወላጆቻቸው
ጭን ላይ ነው፡፡
ኢሚሊ ቡችዋልድ
- ንባብ ዘላቂ ደስታ ያጎናጽፋችኋል፡፡
የአሜሪካ ቀዳሚ እመቤት ላውራ ቡሽ
- ሁሉም አንባቢያን መሪዎች አ ይደሉም፤ ሁ ሉም
መሪዎች ግን አንባቢያን ናቸው፡፡
ሐሪ ኤስ. ትሩማን
- ንባብን ማስተማር ሮኬት ሳይንስ ነው፡፡
ሉዊስ ሞትስ
- የዛሬ አንባቢ፣ የነገ መሪ ነው፡፡
ማርጋሬት ፉለር
- በልጅ ህይወት ውስጥ መፃህፍትን የሚተካ
የለም፡፡
ሜይ ኤለን ቼስ

Published in ጥበብ

የቅጣት ነገር ሲነሳ ትዝ የሚለኝ ጥዋት ጥዋት ሰንደቅዓላማ ለመስቀል ትምህርት ቤት የምንሰለፈውን ሰልፍ ማታ ማታ ለመገረፍ ቤት ውስጥ የምንደግመው ነገር ነው ። ብሄራዊ መዝሙር የተከፈተ ይመስል አባታችን ፊት ያለምንም ንቅናቄ ቀጥ ብለን ባልተዛባ ሰልፍ ቆመን እንገረፋለን። ተራችንን እንኳ አናዛባም።  ብቻ የኔ ትውልድ ከድንጋይ ዘመን ከአፍ ያለ የዱላ ዘመን ትውልድ እስኪመስለኝ ድርስ እናት፣ አባት፣ ጎረቤት በተጨማሪም መምህር ቀጥቅጦ ያሳደገው ነው። ዝናብ ሲመታን “ዝናብ ያሳድጋል” ይሉናል እንጂ ማለት የነበረባቸው “ዱላ ያሳድጋል “ ነበር። ከዝናብ ይልቅ የቀጠቀጠንም ያሳደገንም ዱላው ይመስለኛል።
ከቤት ስጀምር እናቴ ስትቆነጥጠኝ ፊቴ ላይ ያስቀመጠችው የራይት ምልክት ለናይክ የጫማ ፋብሪካ እንደግብአት በማገልገሉ በአሁኑ ሰዓት ታዋቂ የጫማ ማርክ ሆኖዋል ። (እኔን ማስረጃ ይዛ የፈጠራ ውጤቱ ባለቤትነቷን እንድትጠይቅ ብጎተጉታት ጥሩ ይመስለኛል) ሴት የቤተሰቡ አባላት አጭር ቀሚስ እንዳያደርጉ፣ ወንዶቹ በጃፖኒና በቁምጣ እንዳይዘንጡ ማን አስተጓጎላቸው ? እሷ አጠቃላይ ሰውነታችነን ላይ በሰራችው ዲዛይን ምክንያት አይደለምን? “ አርክቴክት ባልሆንና  የህንፃ ዲዛይን ማሰፍርበት ቦታ በሀብት እጥረት ምክንያት ባይኖረኝ ሰፊ ገላ ያላቸው ልጆች አሉኝ” ብላ ተጫወተችብን።
አቤት! በቁንጥጫ ያላስቀመጠችብን ምልክት አለ እንዴ? ህፃን ብትሆንና ለእንቁጣጣሽ ብትሰጠን በስመ አብ በእንቁጣጣሽ አበባ ሽያጭ የከበረች ብቸኛዋ ኢትዮጵያዊት ትሆን ነበር። ምን ያደርጋል እሷም ህፃን አልሆነች እኛም ሰው ሆንባት።
የአባቴ መግረፊያ ጉማሬ የሰንጠረዥ አይነት አሳውቆናል። የኔን ዘልዬ የእህቴን ግርፋት ልንገራችሁ። ቤታችን ውስጥ የተከሰተውን ቁጣ ሸሽቼ እሁድ መዝናኛ ለማየት ጎረቤት ሄድኩ ።
እህቴ ሆዬ እያየሁት ያለሁት እሁድ መዝናኛ አነሰኝ ያልኩ ይመስል፣ ሌላ እሁድ መዝናኛ ይዛልኝ መጣች ። እሷ ስትገረፍ ነበር ወጥቼ የመጣሁት። እሷ ግን ለምን ይቅርበት ብላ ዝንቅ በጆሮዋ ላይ ተሸክማ መጣች። ያበጠ ጆሮዋን ስመለከት ዝንቅ ላይ “ሶስት ጆሮ ያላት የሰው ፍጡር” ብሎ ያቀረቧት መሰለኝ። ጆሮዋ ቅርፁን ሳይለቅ በእብጠቱ እራሱን ደግሟል። የታችኛው ጆሮዋን ይዤ የአዲሱ ጆሮዋን መስማት መቻል ማረጋገጥ ፈልጌ ነበር። እንዴት ልሳቅ? አይኗ ቀልቷል። የሚያምሩኝ ከንፈሮቿ ይዞታቸውን ለቀው የኔን መስለዋል። ለምን መጣች?  ብቻ በሰዓቱ መሳቅም ማልቀስም አልቻልኩም፡፡ ዓይን ዓይኔን ታያለች፤ የታፈነው ሳቄ አፌ ስለተዘጋበት ነው መሰለኝ አፍንጫዬን ያነቃንቀዋል። እንደ ደህና ነገር ሰው ጎረቤት ድረስ መገረፉን ሪፖርት ሊያደርግ ይመጣል?
አይ እህቴ! እቺው እህቴ (እሷን አተኩሬ ምቦጭቅላችሁ አነስ ብላ ቀጠን ያለች ስለሆነች ቀለል ስለምትለኝ ነው) ዱላ ሰልችቷት የኢትዮጵያን ትምህርት ተግባር ተኮር ለማድረግ የጣረችው ነገር ትዝ ይለኛል። እስከ ሰባተኛ ክፍል ከተደበደበች በኋላ ሰባተኛ ክፍል ስትደርስ የስነ ዜጋ ትምህርት ተጀመረላት። ማንም ማንንም የመምታት መብት የለውም ብሎ ሲደበደብ እዚህ የደረሰው መምህራቸው ብሶቱን ተማሪዎቹን ለአብዮት በሚያነሳሳ መልኩ አስተማራቸው።እሜቴ ሆዬ ከታላቅ አጠር ያለ ምክር ፈልጋ ይሁን እኛንም ወደ አብዮቱ ልታካትተን፣ ጉዳዩን መጥታ ለኔና ለታናሽ ወንድሜ አማከረችን፡፡ እኔና ወንድሜ ምንም ሴራ ማሴሪያ ሰዓት ሳያስፈልገን ፈገግ ብለን ከተያየን በኋላ ለአባታችን መንገር እንዳለባት ሹክ አልናት። የሚመጣውን ለውጥ ለማየት ሳይሆን የምትባለውን፣ ከከፋም ቅጣትዋን ለመስማት ጓጉተን ጅል እህታችንን ላክናት።
“ማንም ማንንም የመደብደብ መብት የለውም” እሱዋ ይሄን ስትናገር “የለውም” እያልን በመፈክር መልክ ብናግዛት ደስ ይለን ነበር፤ ግን ሀላፊነቱን እንደ አልቃይዳ ለሷ አሳልፈን ሰጥተን ኮሪደራችን ያለውን ጨለማ ተገን አድርገን የጉባኤው ተካፋይ ሆንን። አባታችን ሳቅ እንደያዘው ያስታውቃል ። ግንባሩን ጨምደድ አድርጎ ሳቁን ለመቆጣጠር ይጥራል። ተሳክቶለታል። ማንም ማን ነው? የሚል ጥያቄ እንዳይከተል የሰጋች ይመስል። የታላቅ ወንድማችንን ስም ትጠራና እሱም ቢሆን እኔን የመምታት መብት የለውም ። ሳጠፋ መምከር እንጂ እንደ አህያ ለምን ይቀጠቅጠኛል ? መልስ ስታጣ ድምጿ መርገብገብ ጀመረ። “የምሸሸግበት ጥግ አጣሁ እመብርሃን” ሳትል ትቀራለች። ለውጥ ባታመጣም በቅጣቱ ሂደት ላይ የማሻሻያ ስራ እንደሚሰራበት ቃል ተገብቶላት ወጣች። እኛም ባንዲራውን ከፍ አድርጎ እንዳውለበለበ ጀግና አቀባበል አደረግንላት። ይገባታል። ታሪክ መለወጥ ባትችል ታሪክ ለመስራት የሞከረች አዲስ ትውልድ!
እናታችን በቁንጥጫ፣ አባታችን በጉማሬ፣ መምህር በዱላ አሊያም በጎማ የሚገርፉን  ሁሌ አንድ አይነት ሆኖ እንዳይሰለቸን በአቅራቢያ ከሚገኙ ዛፎች ዘንጥፈን ወይም ዶቢ በአዲስ አበባ ስሟ ሳማ ቆርጠን ይዘን እንድንመጣ እንታዘዛለን። ያኔ እርግብ ነበርን፤ የታዘዝነውን ይዘን እንመለሳለን፡፡ ይሄን ሳስብ ቁራ ይገርመኛል። መገረፊያ ይዘህና አልተባለ፤ ሄደህ ውሃው መድረቁን አይተህ ና ለተባለው በዛው መቅረቱ! አሁን እንደው ዶቢ ይዘና ቢባል ምን ሊሆን ነው ? እስከነ አካቴው ምድር ላይ የቁራ ዘር ሊጠፋ ይችል ነበር። ብቻ ቁራ የኛ ቤት ነዋሪ ሊሆን የሚያስችል አንድም ባህሪ አላየሁበትም ።
ወላጅ ያኔ ገርፎ የሚደክመው እንጂ ቅጣቱ የሚወጣለት አይመስለኝም፡፡ መምህራኖችን ባገኘበት አጋጣሚ “እንደው አደራህን ልጄን እየቀጣህ” ብሎ ትእዛዝ ይሰጣል። ያም መምህር ተባለም አልተባለም መቅጣቱ ባይቀርም ትውውቅ እንዳለው ለማሳወቅ በትንሹም በትልቁም ዱላው እረፍት እንዳያገኝ ይሰነዝራል። ከኔ ዘመን ርቆ ያለው ትውልድ ከዱላ ጋር ብዙም እውቂያ ያለው አይመስለኝም። እንደኔ ለምን ሳይቀጠቀጥ ቀረ ብዬ አይደለም። ግን ሲያጠፋም ወላጅ አይቀጣውም፤ መምህር ምርር ብሎት “ይህን ትውልድ ለማነፅ ትንሽ ቅጣት ያስፈልጋል” ብሎ እጁን ቢሰነዝር፣ ወላጅ በነጋታው ይመጣና እሱ ግንባር ላይ አነስ ያለች “ፒስትል” ይሰነዝራል።





Published in ህብረተሰብ
Page 7 of 17