ብዙ የናፈቁን ዜናዎች አሉ!

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሁለቱ ልጆች እያወሩ ነው፡፡ አንደኛው ልጅ ምን ይላል… “አባዬ የሁሉም ነገር ዋጋ እየጨመረ ነው ሲል ሰማሁት፡፡”
“ምንድነው የጨመረው?”
“የምግብ፣ የልብስ፣ የቤት ኪራይ ሁሉ ጨምሯል አለ፡፡ ደግሞ ምን አለ መሰለህ!”
“ምን አሉ?”
“የሆነ ነገር ቁጥሩ ቀንሶ ማየት ጓጉቻለሁ አለ፡፡”
ጓደኝየው ምን ቢለው ጥሩ ነው… “ግዴለም፣ የአንተን ሰርተፊኬት ሲያዩ በደንብ የሚቀንስ ቁጥር ያገኛሉ፡፡
ሀሳብ አለን…የኑሮ ማስተካከያ ይደረግልን፡፡ ልክ ነዋ…ለምንም ነገር ማስተካከያ ይደረግ የለም አንዴ!
እናላችሁ…ሥጋ እንኳን በሩብ ኪሎ መሸጥ መጀመሩን ወዳጄ ሲያጫውተኝ ነበር፡፡ እየደረስን ያለንበትን ዘመን እዩልኝማ፡፡ ገና በኪሎና በግራም መለካቷ ቀርቶ በጉርሻ ሊሆን ይችላል፡፡ “ሁለት ጉርሻ ሥጋ ስጠኝ…” ማለት እንጀምር ይሆናል! አይሆንም የሚባል ቃል እየጠፋ ያለባት አገር ነቻ!
እናማ…የኑሮ ማስተካከያ ይደረግልን፡፡
ስሙኝማ…በቲቪ ላይ እኮ የምግብ አሠራር እያየን መጎምጀት ከተውን ከረምን፡፡ ልክ ነዋ… ቦምቦሊኖ ባረረብን ዘመን የምናየው ሁሉ እንቁልልጭ ሆነብና!
የምር ግን… አለ አይደል… የፈጠራ ጊዜ አሁን ነው። በሬድዮና በቲቪ ስለምግብ አሠራር የምታስተምሩን ፈጠራ ቢጤ ጨምሩበታ፡፡ ለምሳሌ ‘ያለበርበሬ ቀይ ወጥን መሥሪያ ዘጠኝ ዘዴዎች’ አይነት ነገር። ደግሞላችሁ… ‘ሹሮ ሽንኩርትና ዘይት ሳይገባባት ውሀና ሹሮዋ ብቻ ተበጥብጠው ጣት የሚያስቆረጥም ወጥ የመሥሪያ ምስጢሮች…’ የሚል ፈጠራ፡፡ ልክ ነዋ…ትንሸ ቆይተን ጣት የምንቆረጥመው ምግብ ስለጣፈጠን ሳይሆን ጉርሻችን ከማነሷ የተነሳ ጣት እየተቀላቀለችብን ሊሆን ይችላል፡፡
ሀሳብ አለን…የምግብ አሠራር የቲቪ ትምህርቱ በመደብ ይከፋፈልልን፡፡ አለ አይደል…
‘በወር አንዴ ሥጋ ለሚበሉ…’
‘በወር አንዴ ሥጋ በህልማቸው ለሚያዩ…’
‘በወር አንዴ ሥጋ የሚባለው ቃል መዝገበ ቃላት ላይ መኖሩ ትዝ ለሚላቸው…’  በሚል መደብ ይከፋፈልልን። ወይንም እንደ ግብር ከፋዮች ‘ሀ’ ‘ለ’ እና ‘ሐ’ ተብለን እንከፋፈል፡፡፡ “የዛሬው የምግብ አሠራር ለ‘ለ’ ምድቦች ብቻ የሚሆን ነው…” ስንባል ቁርጣችንን አውቀን አርፈን እንቀመጣለና!
እናላችሁ… ዘንድሮ… አለ አይደል… “አንተ ምነው ባለቤትህ ከሳችብኝ!” ብሎ አስተያየት አሪፍ አይደለም። አሀ…ነገርዬው ሁሉ ‘ጣራ ነክቶ’ እንዴት ትወፍር! በፊት እኮ “በሽታ እንኳን ያወፍራል…” ይባል ነበር፡፡ ዘንድሮ ኩሽናው ሁሉ ምነዋ ይሄን ያህል መአዛ የለውሳ!
እናማ… “አንተ ምነው ባለቤትህ ከሳችብኝ!” ብሎ አስተያየት ‘ወቅቱን ያላገናዘበ’ ይሆናል፡፡ አሀ… በብር ሦስትና አራት ይገዛ የነበረ እንቁላል አንዱ ሦስት ብር ከሀምሳ ሳንቲም ምናምን ሲሆን እንዴት ሆና ‘ሥጋ’ ታውጣ፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ባል ራሱ ‘አርፎ አይቀመጥ’!  ቂ…ቂ…ቂ….
እኔ የምለው…“ዳየት ላይ ነኝ…” ምናምን የምትሉ እንትናዬዎችን ሌላ ሰበብ አምጡማ፡፡ ኑሮ ራሱ ሁላችንንም ‘ዳየት ላይ’ አድርጎናላ! እናማ…‘ዳየት ላይ’ መሆኑ የግዴታ እንጂ የውዴታ ባልሆነበት…“ዳየት ላይ ነኝ…” አይነት ምክንያት አይሠራም፡፡
ስሙኝማ…በፊት የሆነ ነገር ዋጋው ጣራ ነካ ሲባል የሆነ መሥሪያ ቤት ለ‘ፐብሊክ ኮንሰምሺን’ ለሚሉት ነገርም ቢሆን… “የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት ሥራዎች እየተሠሩ ነው…” ምናምን  የሚባለው ‘ልብ አንጠልጣይ ልብ ወለድ’ እንኳን አሁን፣ አሁን እየቀነሰ ነው፡፡
“እነሱ አንድ ነገር ያደርጉልናል…ዋጋውን ወደ ቦታው መልስው ያረጋጉልናል…” ስንል ተስፋ ቆረጡ እንዴ! አሀ…ወንበር ብቻ ሳይሆን ዋጋም ይረጋጋልና!
እናማ…“በተለይ በምግብ ሸቀጦች ላይ የሚደረገውን ምክንያተ ቢስና ኢፍትሀዊ ዋጋ ንረት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስተካከል የማያዳግም እርምጃ መውሰድ ሊጀመር ነው…” አይነት ዜና መስማት ናፍቆናል፡ ልከ ነዋ…በሆዳችን ‘ድንቄም ተወሰደ!’ ብንል እንኳን ለጊዜውም ቢሆን ለጆሯችን አሪፍ ዜማ ይሆናላ!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ልንሰማቸው የናፈቁን ዜናዎች መአት ናቸው…
‘ከወሩ መግቢያ ጀምሮ በመላ አገሪቱ የጤና አገልግሎት ሙሉ፣ ለሙሉ ነጻ ሆኗል…’
‘ከመጪው ሰኞ ጀምሮ አንድ ኩንታል ጤፍ ከአምስት መቶ ብር በላይ ሲሸጥ የተገኘ ነጋዴ ፈቃዱ ተነጥቆ ከመፋቂያ በላይ የሆነ ምርት እንዳይሸጥ የአራተ ዓመት እገዳ ይጣልበታል…’
‘በበዓላት ወቅት ቀበሌዎች ቤት ለቤት እየዞሩ ኪሎ ቅቤ በሀያ አምስት ብር ማከፋፈል ይጀምራሉ…’
‘የአንድ ኪሎ በርበሬ ከፍተኛ ዋጋ አሥራ አምስት ብር ከሃያ አምስት ሳንቲም እንዲሆን እንትን መሥሪያ ቤት ወሰነ…’
‘ከፍተኛ ባለስልጣኖች በአሥራ አምስት ቀን አንድ ጊዜ መርካቶና ሾላ ገበያ እየሄዱ ራሳቸው እንዲገበዩ የውዴታ ግዴታ ተጥሎባቸዋል…’ (ያን ጊዜ…አለ አይደል…“እንዲህም የሚኖር ሰው አለ!” ይሉ ነበር፡፡)
እንደ እነዚህ አይነት ‘ዜናዎች’− “ካልተረጋገጡ የወሬ ምንጮች…” እንኳን− የምንሰማበት ዘመን ይመጣ ይሆን! መመኘትም የ‘ክላስ’ ጉዳይ እስኪሆን ድረስ እኛም እንመኝ እንጂ!
ካነሳነው አይቀር…ሌሎች የናፈቁን ዜናዎች አሉ…
‘እንትንና እንትን ድርጀቶች ከእንግዲህ መዘላላፍና ትርፍ ቃላት መወራወር ትተው ቁም ነገር ላይ ለማተኮር ተስማምተዋል…’
‘ባለስልጣኖች ለሜዲያ መግለጫ በሚሰጡበት ጊዜ የማስፈራሪያና የንቀት ቃላት ሲናገሩ ቢገኙ የተሰጣቸውን ወንበርና የተሰጣቸውን ቤተ ይነጠቃሉ…’ (ቂ…ቂ…ቂ…. ታየኝ!)
‘በሆነ ባልሆነው ትንሹንም ትልቁንም የሚዠልጡ ስነ ስርአት አስከባሪዎች በእጃቸው አርጩሜ እንኳን እንዳይዙ ይከለከላል…’
አሪፍ አይደል! ያኔ እንዴት አይነት ‘ነፍስ የሆንን’ ሰዎች ይወጣን ነበር፡፡
ደግሞላችሁ ሌሎች የናፈቁን ዜናዎች አሉ…
‘የሰው ሚስት የሚያማግጥ ጭቃ ሹም ሆነ ምስለኔ አይደለም ሴት፣ የሴት ፎቶ የማያይበት በረሀ ለአምስት ዓመት እንዲቀመጥ ይገደዳል…’
‘ሥራ አስኪያጆች ኤክሲኪዩቲቭ ሴክሬታሪዎችን ፊት ለፊት በአካል ሳይሆን በስልክ ብቻ እንዲያገኙ ተወሰነ…’ (ቂ…ቂ…ቂ…)
‘በየመጠጥ ቤቱ መቶና መቶ ምናምን ብር ለመክፈል የመለስተኛ መሥሪያ ቤት ተከፋይ ደሞዝ የሚመስል የብር መአት የሚመዙ ሰዎች ሌላው ተገልጋይ ላይ ለሚደርሰው ማንኛውም የብሽቀት፣ የመጎምጀት፣ የደም ብዛት ችግር ሁሉ ተጠያቂ ይሆናሉ…’
‘ከእንትናዋ ጋር የምትሄደውን እንትናዬ ከሦስት ሰከንድ በላይ ትክ ብለው የሚያዩ ባለመኪኖች መኪናቸውን ተነጥቀው ለአሥራ አንድ ወር በእግራቸው ብቻ እንዲሄዱ ይደረጋሉ…!’ የሚል ዜና ናፍቆናል፡፡ (እግረኞቹ ሁሉ እየተሳቀቁ አሳዘኑና!)
መአት ልንሰማቸው የምንፈልጋቸው ዜናዎች አሉ፡፡ “ሰበር ዜና…ዋጋዋ አልቀምስ ብሎ ሃያ ምናምነኛ ፎቅ ላይ የወጣችው ቲማቲም አንድ ኪሎ በብር ተሀምሳ እንደገባች ተገለጸ…” አይነት ዜና መስማት ናፍቀናል፡፡
“ከፍተኛ የአገሪቱ ባለስልጣናት በመርካቶ፣ በአትክልት ተራና በሾላ ገበያ ባደረጉት ጉብኝት ባዩት የምግብ ግብአቶች ዋጋ ከፍተኛ ድንጋጤ እንዳደረባቸው ምንጮቻችን ገለጹ፡፡ በተለይ አንዱ ባለስልጣን… ‘ኑሮ ይህን ያህል መክበዱን በህልሜም ጠርጥሬ አላውቅም፡፡ ዕንባዬ ነው የመጣው…’ ማለታቸው ተዘግቧል…” አይነት ዜና ናፍቆናል፡፡
የኑሮ መክበድን በተመለከተ ብዙ ልንሰማቸው የምንፈልጋቸው ዜናዎች አሉ፡፡
የከበደውን ኑሮ የሚያቀልልን ዘመን ያፍጥልንማ!
ጀርባችን ሳይሰበር፣ ሰማይ የወጣውን የሸቀጦች ዋጋ የሚሰብር ተአምር ይላክልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Published in ባህል

ከዕለታት አንድ ቀን እመት ጦጢት ምግብ ስትሰራ እንስሳት አገኟትና፤
“እመት ጦጢት?”
“አቤት” አለች፡፡
“ሽሮና በርበሬ ማን ያመጣልሻል?” አሏት፡፡
“ባሌ” አለች
“ከየት ያመጣል?”
“ሠርቶ፣ ወጥቶ፣ ወርዶ”
“ሰርቆስ እንደሁ የሚያመጣው በምን ታውቂያለሽ?”
“አምነዋለሁ”
“ቂቤስ ከየት አመጣሽ?”
“ባሌ አመጣልኝ”
“ከየት ያመጣል?”
“ሰርቶ፣ ወጥቶ - ወርዶ”
“ሰርቆስ እንደሁ በምን ታውቂያለሽ”
“ባሌን አምነዋለሁ”
“ከዕለታት አንድ ቀን ሌላ ጦጢት ይዞብሽ ቢመጣስ?”
“ተገላገልኳ! አጋዥ አገኘሁ፡፡ እሷ ምግብ ትሰራለች፤ እኔ እሱን አቅፌ እተኛለሁ”
“እስከ ዛሬ ጦጣ ብልጥ ናት ሲባል ነበር፡፡ ለካ አንደኛ ደረጃ ጅል ነሽ?!”
“ጅልስ እናንተ፡፡ እየሰረቃችሁ መዋችላሁ አንሶ ወደሌላ ለማዛመት ሌብነት፣ ከቤት - ቤት ይዛችሁ የምትዞሩ!! በሉ ሌብነታችሁን ሌላ ቤት ይዛችሁልኝ ሂዱ!” ብላ ከቤት አስወጣቻቸው፡፡
*   *   *
እንደ ጦጣ አለመመቸት ብልጥነት ብቻ ሳይሆን ብልህነትም ነው!
ጥርጣሬ፣ ቅጥፈትና ሌብነት አንድ ህብረተሰብ ውስጥ ሲነግሥ ዕድገት መቀጨጩ አሌ አይሉት ነገር ነው፡፡ የተዋሃደውን ለመነጣጠል፣ የተጋባውን ለማፋታት፣ የተደራጀውን ለመበታተን መሞከርን ያህል እኩይ ተግባር ያጥጣል። የተማረው እንዳልተማረ ይናቃል፡፡ የመንገዱን መነሻ እንጂ መድረሻውን አለማስተዋል የዕለት የሰርክ ህፀፅ ይሆናል፡፡
ሮበርት ግሪን፤
“ፍፃሜውን የማትገምተው ነገር አትጀምር” ይለናል፡፡
ያቀድነው ዕቅድ ከየት ያስጀምረናል? ወዴት ያመራናል? ወዴትስ ያደርሰናል? ግብዐቶቹ ምን ምንድናቸው? ብሎ በቅጥ በቅጡ እያዩ መከታተል፤ እናም እፍፃሜ ሳይደርስ ሌላ ምዕራፍ አለመጀመር፣ በተለይ ትግል ውስጥ ለገባ ቡድን፣ ስብስብ፣ ማህበር ወይም ድርጅት፤ ዋና ነገር ነው፡፡ ሁለተኛው በቂ ዝግጅት ማድረግ ነው። ባጭሩ በአገርኛ ግጥም፡-
“ቀድሞ ነበር እንጂ፣ መጥኖ መደቆስ
አሁን ምን ያደርጋል፣ ድስት ጥዶ ማልቀስ” የሚለውን ማስታወስ ነው፡፡
“ሌሎች አዝመራውን ስለሚሰበስቡት ሰብል ማለም ከንቱ ህልም ነው፡፡ ይልቅ ራስህ መጨረሻውን የምትጨብጠውን ህልም ዛሬውኑ አልም!” ይላሉ አበው፡፡
ህልማችን ዕውን እንዳይሆን እፊታችን የሚደቀኑትን እንቅፋቶች ለይቶ ማስቀመጥ፣ እንቅፋቶቹን አልፎ ለመሄድ የሚገባውን ያህል አቅም መፍጠርና ጉልበትን ማጠራቀም፤ ሳይታክተን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ፣ በፅናት መጓዝ፤ ያስፈልጋል፡፡ ምንጊዜም ቢሆን ሙሉ በሙሉ ማሸነፍና ሙሉ ለሙሉ መሸነፍ አለመኖሩን፣ ማመንና ይልቁንም፤ ጠንካራና ደካማ ጎን ሁሌም መኖሩን ማስተዋል የተሻለ ዕውነታ ነው፡፡
ሁኔታዎች ተለዋዋጭ መሆናቸውንና አዲስ አሸናፊ ምንጊዜም መብቀሉን ለአፍታም አለመዘንጋት ነው፡፡ ተስፋ አለመቁረጥ የሚመነጨው ከዚህ ዕሳቤ ነው። ያለ ሁሌም የሚኖር ይመስለዋል፤ ይላሉ አበው፡፡ ሆኖም ያልፋል፤ ማለታቸው ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የፍትህ አካላት፣ የአስተዳደር ወኪሎች እና ፍርድ ቤቶችም ጭምር፣ ከህብረተሰብ ጋር የሰፋ ግንኙነት መፍጠርና በመዋቅርም፣ በመንፈስም የበለጠ ዲሞክራሲያዊነት እንዲኖራቸው መጣር፤ ዛሬ የዓለም ሁሉ ትጋት ነው፡፡ ከዚህ የድርሻችንን መውሰድ ነው፡፡ ክሊንተን ሮዚተር የተባለው ምሁር፤ “አገር ያለ ዲሞክራሲ፣ ዲሞክራሲ ያለ ፖለቲካ፣ ፖለቲካ ያለ ፓርቲዎች አይኖርም” ይለናል። ይህን እንዲሰራ ለማድረግ ግን ቀና ልቡና ይጠይቃል፡፡ ጤናማ ፓርቲና ጤናማ ፖለቲካዊ ስነ - ልቦናም እነዚህ ውስጥ ወሳኝ ናቸው፡፡ ያሉት ቀና ፓርቲዎች እጅግ ጥቂት ናቸው፡፡  ያሉንን የፖለቲካ ፓርቲዎች ካመናመንንና ካጠፋናቸው     “ከርከሮ አንዲት ፀጉር አለችው፣ እሷን ለማጥፋት ይተሻሻል” የሚለውን ተረት በታሳቢነት ያዝን ማለት ነው፡፡

Published in ርዕሰ አንቀፅ

በልጅነታቸው ፖለቲከኛ የመሆን ህልም አልነበራቸውም
ወንድሞቻቸው በሙሉ ከመጀመሪያ ድግሪ በላይ የተማሩ ናቸው
ጠ/ሚኒስትሩ ለእናታቸው የተለየ ፍቅር አላቸው

ባለፈው ሳምንት ከአዲስ አበባ በ385 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል፣ ቦሎሶሶሬ ወረዳ ሶሬ አምባ ቀበሌ ውስጥ የተገኘሁት ለሌላ የስራ ጉዳይ ነበር፡፡ እንደሚታወቀው ሥፍራው የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ የትውልድ ቀዬ ሲሆን በዘንድሮው አገር አቀፍ ምርጫም የተወዳደሩበት ሥፍራ ነው፡፡  ዕድል ቀንቶኝ ታዲያ
የጠ/ሚኒስትሩን ታናሽ ወንድም አቶ ደረጀ ደሳለኝን ለማነጋገር ቻልኩኝ፡፡
አቶ ደረጀ ሁለተኛ ድግሪያቸውን በሂዩማን ኒውትሪሽን ፐብሊክ ኸልዝ ለላይ እየሰሩ መሆናቸውን ነግረውኛል፡፡ ቆይታችን ያተኮረው ግን በታላቅ ወንድማቸው በጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ዙሪያ ነበር፡፡
የዛሬው ጠ/ሚኒስትር ለቤተሰቦቻቸው እንዴት ያለ ልጅ ነበሩ? የተማሪነት ህይወታቸው ምን ይመስላል? ሥልጣን ከያዙ በኋላ ከቤተሰባቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት ምን መልክ ያዘ? እኒህንና ሌሎች ታሪኮችን ከታናሽ ወንድማቸው ከአቶ ደረጀ ደሳለኝ አንደበት እንከታተል፡-

         ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማርያም ለቤታችሁ ስንተኛ ልጅ ናቸው? የልጅነት ህይወታቸውስ ምን ይመስላል?
እሱ ለቤታችን የመጀመሪያ ልጅ ነው። በአጠቃላይ ዘጠኝ ልጆች ነን ያለነው፤ አንዲት ሴትና ስምንት ወንዶች፡፡ እሱ የሁላችንም ታላቅ ነው፡፡ የልጅነት ህይወቱን በጥልቀት ለመናገር እቸገራለሁ፡፡ እኔ የቤቱ የመጨረሻ ልጅ ነኝ፡፡ ግን አባ (ኃይለማርያም) በልጅነቱ በባህርይው የተረጋጋ፣ ትምህርቱን አጥብቆ የሚወድና ጥሩ ሥነምግባር የነበረው ልጅ እንደነበር አውቃለሁ፡፡ ጊዜውን በእረፍትና በመዝናናት  ለማሳለፍ የማይፈልግ ሥራ ወዳድ እንደነበር ወላጆቻችን በተደጋጋሚ ሲናገሩ ሰምቻለሁ፡፡ ለሁላችንም ምሣሌ ሆኖን ነው ያደግነው፡፡
ትምህርታቸውን የት ነው የተከታተሉት?
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ቡበቃ ሰልቃይንት እየተባለ በሚጠራ የካቶሊክ ሚሽን ት/ቤት ውስጥ ነው የተማረው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በወላይታ ሶዶ ሊጋባ ት/ቤት ተከታተለ፡፡  ከዚያም በከፍተኛ ውጤት ለዩኒቨርሲቲ በቃ፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢንጅነሪንግ ሲመረቅ በከፍተኛ ማዕረግ የሜዳልያ ተሸላሚ ነበር፡፡ ከዚያም በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ተቀጠረ፡፡ ሁለተኛ ድግሪውን በፊንላንድ ተምሮ ከመጣ በኋላ በአርባምንጭ ዩንቨርሲቲ የወተር ቴክኖሎጂ ዲን በመሆን አገልግሏል፡፡
የተማሪነት ህይወታቸውን እንዴት ነው ያሳለፉት?
በጣም ከባድ ህይወት ነበር፡፡ በተለይ ከአባታችን ሞት በኋላ ሁሉም ነገር እጅግ ከባድ ሆነ፡፡ አባታችን በአንድ የካቶሊክ ሚሽን ት/ቤት ውስጥ በአስተማሪነት ይሠራ ነበር፡፡ የምንተዳደረው በግብርና ቢሆንም አባታችን  በማስተማር በሚያገኘው ገቢ ነበር ብዙውን ነገር የሚሸፍነው፡፡ እናታችን የቤት እመቤት ናት፡፡ በግብርና ሥራው ከመሳተፍ ውጪ ሌላ ገቢ አልነበራትም፡፡ እናም የቤተሰቡ የገቢ ምንጭ የነበረው አባታችን በ1975 ዓ.ም በህመም ምክንያት ሲሞት ቤተሰባችን ለከፍተኛ ችግር ተጋለጠ፡፡ ያን ጊዜ ደግሞ ኃይለማርያም ወደ ዩኒቨርሲቲ ያለፈበት ጊዜ ነው፡፡ እናም ለእኛ መጥፎ ወቅት ነበር፡፡
ይህንን ክፉ ጊዜ ያለፍነው በዘመዶቻችን እርዳታና ድጋፍ ነበር፡፡ በወቅቱ ኃይለማርያም ተማሪ በመሆኑ ምንም ሊያደርግልን የሚችልበት ሁኔታ ውስጥ አልነበረም፡፡ በልጅነታችን በርካታ ውጣ ውረዶችን አይተን ነው ያደግነው፡፡ የረዥም ሰዓት የእግር መንገድ እየሄድን ነበር የምንማረው፡፡  በእኛ ህይወት ውስጥ የእናታችን ድርሻ ከፍተኛ ነው፡፡ እሷ ሳትማር እኛን አስተምራ ለዚህ ደረጃ በማድረሷ በማድረጓ የላቀ ምስጋና ይገባታል፡፡
አቶ ኃይለማርያም በታናናሾቻቸው ህይወት ውስጥ ምን ቦታ አላቸው?
በጣም ትልቅ ድርሻ አለው፡፡ እንደነገርኩሽ ከአባታችን ሞት በኋላ ኑሮ ለእኛ እጅግ ከባድ ነበር፡፡ ያን ጊዜ አባ (ኃይለማርያም) ወደ ዩኒቨርሲቲ ያለፈበት ጊዜ ስለነበር ምንም የማድረግ አቅም አልነበረውም። ተመርቆ ሥራ ከያዘ በኋላ ግን ወደ ከተማ ሄደን ትምህርታችንን እንድንከታተል ብዙ ጥረት አድርጓል። ታላላቅ ወንድሞቼን አርባ ምንጭ ድረስ ወስዶ አስተምሮአቸዋል፡፡ እንደ ታላቅ ወንድምም እንደ አባትም ሆኖ ነው ያሳደገን፡፡ ለዚህም ነው ሁላችንም አባ እያልን የምንጠራው፡፡
በወጣትነታቸው የፖለቲካ ፍላጐት ነበራቸው? ወደ ፖለቲካው ዓለም የመግባት ፍንጮች ይታይባቸው ነበር?
ዝርዝሩን ባላውቅም ወደ ፖለቲካው ዓለም ይገባ ይሆናል የሚያሰኙ ምልክቶች ግን እንዳልነበሩት አውቃለሁ፡፡ ይህንን አስቦ ቢሆን ኖሮ ትምህርቱም ወደ ፖለቲካው ሣይንስ ያደላ ይሆን ነበር፡፡ እሱ እንደውም ማጥናት የሚፈልገው ሜዲስን (ህክምና) ነበር፡፡ የፖለቲካ ፍላጐት ግን እንጃ አይመስለኝም፡፡ በእርግጥ በወቅቱ የነበረውን የግል ፍላጐት በጥልቀት ለማወቅ ይቸግረኛል፡፡
ታዲያ ለምን ሜዲስን (የህክምና ሙያ) አላጠኑም?
በአጋጣሚ ነው፡፡ አባታችን ታሞ ጥቁር አንበሣ ሆስፒታል ተኝቶ ሳለ ያስታምመው እሱ ነበር፡፡ በዚያ ወቅት የህክምና ሙያ ምን ያህል ከባድና አስቸጋሪ እንደሆነ በመገንዘቡ ሜዲስን የማጥናት ፍላጐቱን ገታው፡፡ እናም ትምህርቱን በኢንጅነሪንግ ሙያ ለመቀጠል ወሰነ፡፡
የሌሎቻችሁ የትምህርት ደረጃስ ምን ይመስላል?
ዘጠኛችንም ከመጀመሪያ ድግሪ በላይ ተምረናል። አንደኛው ወንድማችን በቅርቡ የፕሮፌሰርነት ማዕረጉን ወስዷል፡፡ በአዋሣ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ዲንና ምክትል ፕሬዚዳንት ሆኖ እየሠራ ነው። ፕሮፌሰር ፍቅሬ ደሳለኝ ይባላል፡፡ እህታችን በኢኮኖሚክስ ሁለተኛ ድግሪዋን ሰርታ፣ አዲስ አበባ ፔትሮሊየም ድርጅት ውስጥ ተቀጥራ እየሠራች ትገኛለች፡፡ ትዕግስት ደሣለኝ ትባላለች። በኤሌክትሪካል ኢንጅነሪንግ ማስተርሱን ጨርሶ፣ አዲስ አበባ የአይሲቲ ምክትል ማናጀር ሆኖ የሚሰራ ገነቱ ደሳለኝ የሚባልም ወንድም አለን፡፡ በነርሲንግ ማስተርሱን ይዞ በዲላ ዩኒቨርሲቲ ሜዲሲን (ህክምና) በመማር ላይ የሚገኘው ሌላው ወንድማችን ብሥራት ደሳለኝ ይባላል፡፡ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በፐብሊክ ኸልዝ ማስተርሱን እየተማረ የሚገኝ ዳዊት ደሳለኝ የሚባል ወንድም አለን፡፡
ወደ ፖለቲካ ዓለም ያደላው አንድ ወንድማችን በአረካ ወረዳ የወረዳው የፖለቲካ አደረጃጀት ኃላፊ ሆኖ እየሰራ ነው፤ ማርቆስ ደሳለኝ ይባላል፡፡ እኔም ሁለተኛ ዲግሪዬን በሒዩማን ኒውትሪሽን ፐብሊክ ኸልዝ ላይ እየሰራሁ ነው፡፡ አሁን የመመረቂያ ጽሑፍ እያዘጋጀሁ ነው፡፡ በአጠቃላይ ሁላችንም ከመጀመሪያ ድግሪ በላይ በሆነ ደረጃ ትምህርታችንን ተከታትለናል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ትውልድ ቀዬአቸው ሲመጡ ከቤተሰቦቻቸውና ከአብሮ አደግ ጓደኞቻቸው ጋር በነፃነት የሚገናኙበት ሁኔታ አለ?
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደልብ የመገናኘቱ ጉዳይ የለም፡፡ በነፃነት መንቀሳቀስ አይችልም፡፡ ድሮ በክርስትና ህይወቱ እንደልቡ ወደ ቸርችም ይሄድ ነበር። አሁን ግን እንደሱ የለም፡፡ ሁሌ እንደፈለገ መሆን አይችልም፡፡ የእነሱ ሥራ የሴኩዩሪቲ ሥራ ስለሆነ ጥንቃቄን የሚፈልግ ነው፡፡ እንደ ድሮ መሆን የለም፡፡
ከእናታቸውስ ጋር ይገናኛሉ?
አዎ፡፡ ለእናቱ የተለየ ፍቅር ነው ያለው፡፡ እሷም እንደዚያው ናት፡፡ ከድሮ ጀምሮ ከዩኒቨርሲቲ ሲመጣ በተለየ ሁኔታ ነበር የምትቀበለው፡፡ እሷ አሁንም ያው ናት፡፡ ለእሷ አሁንም የያኔው ልጇ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን አለመሆኑ በእሷ ላይ ምንም ለውጥ አላመጣባትም፡፡ ታላቅ ከመሆኑም አንፃር ሁላችንም እናከብረዋለን፡፡ እንታዘዝለታለን፡፡ እናም ወደዚህ የሚመጣበት ጉዳይ ሲኖር እናቱን ሳያገኝ አይመለስም። በጣም ይወዳታል፡፡ ለሁላችንም እዚህ መድረስ እሷ የከፈለችው ዋጋ ከፍተኛ ነው፡፡ እንደ አርሶ አደር አርሳ፣ ሳንራብ እንድናድግ ያደረገችው አስተዋጽኦ በቀላሉ  የሚገመት አይደለም፡፡ እናም ለእሷ የተለየ ፍቅር አለው፡፡ ትንሽ ከታመመች ወደ አዲስ አበባ ሄዳ ሕክምና እንድታገኝ ያደርጋታል፡፡
እናንተስ ወደ አዲስ አበባ ስትመጡ ከወንድማችሁ ጋር የምትገናኙት እንዴት ነው? በስልክስ የመነጋገር ዕድል አላችሁ?
እሱ የራሱ ስልክ የለውም፡፡ እኛ ደውለን ማግኘት የምንችለው በባለቤቱ በኩል ነው፡፡ እሱ ግን ደውሎ እናቱን አነጋግሮ ሲጨርስ፣ እኛንም በየተራ ያነጋግረናል። ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ በፈለግን ጊዜ አስቀድመን ደውለን ፕሮግራም እናስይዛለን። መምጣታችንን አስቀድመን አሣውቀን መኪና ይላክልንና ያለ ብዙ ፍተሻ እንድንገባ እንደረጋለን፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከባለቤታቸው ጋር የት ተገናኙ? ጋብቻቸውስ እንዴት ነበር?
በዩኒቨርሲቲ ህይወት እንደተገናኙ ነው የማውቀው፡፡ ጓደኝነታቸውም እዚያው የተጀመረ ነው፡፡ ጋብቻቸውን የፈፀሙት በሠርግ ነው። ሰርጋቸው ሶርአምባ ወይንም በእኛ የትውልድ ቦታ ላይ ነው የተደረገው፡፡ በመንፈሳዊ ሥነስርዓት ቃልኪዳን ፈጽመው ነው የተጋቡት፡፡ ጊዜው በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ ነው፡፡
ስንት ልጆች አፍርተዋል? ልጆቹ በምን ደረጃ ላይ ይገኛሉ?
ሶስት ሴት ልጆች ነው ያላቸው፡፡ ሁሉም በጥሩ ደረጃ ላይ እየተማሩ ነው የሚገኙት፡፡  አንደኛዋ በአምስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ የኢንጅነሪንግ ተማሪ ነች፡፡ ሌላዋ በስኮላርሽፕ ወደ አሜሪካ ሄዳ እዚያ እየተማረች ነው፡፡ አንደኛዋ (ኩኩ) እሷም እንዲሁ ትምህርቷን በመከታተል ላይ ትገኛለች፡፡
የልጆቹ ባህርይ እንዴት ነው?
ልጆቹ በሚያስገርም ሁኔታ ራሳቸውን ዝቅ የሚያደርጉ፣ ትሁቶችና ፍፁም በጥሩ ሥነምግባር የታነፁ ልጆች ናቸው፡፡ እኛ እንኳን ወደ እነሱ ጋ በምንሄድበት ወቅት እንደዘመኑ ልጆች በራሳቸው ጉዳይ ተጠምደው፣ እኛን የሚረሱ ልጆች አይደሉም። ፍፁም ትሁት በሆነ መንገድ ተቀብለው ነው የሚያስተናግዱን፡፡
ወደ አዲስ አበባ መጥታችሁ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በምትገናኙበት ወቅት ቆይታችሁ ምን ይመስላል?
ቤት ሄደን ከእነሱ ጋር ስንገናኝ በጣም ደስ የሚል ጊዜ ነው የምናሳልፈው፡፡ ወንድማችን ከቤተሰቦቹ ጋር መጫወትን አጥብቆ ይወዳል፡፡ ያለፈውን ነገር፣ የድሮውን ሁኔታ እያነሳን እንስቃለን፡፡ ደስ የሚል ቤተሰባዊ ጊዜን ነው የምናሳልፈው፡፡ ሁላችንም እንዲህ ያለውን አጋጣሚ በእጅጉ እንናፍቀዋለን፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩን እንዴት ይገልፁዋቸዋል?
ሰው ከባዶ ነገር ተነስቶ በጥንካሬ ትልቅ ቦታ መድረስ እንደሚችል በማሳየት፣ ለሁላችንም ትልቅ ሞዴል ለመሆን ችሏል፡፡ በግል ደግሞ እንደ ታላቅ ወንድምም እንደ አባትም ሆኖ ያሳደገን ትልቅ አርአያ የምናደርገው ሰው ነው፡፡ የአንድ ሰዓት የእግር መንገድን ተመላልሶ ተምሮ እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ ሊታመን የማይችል ትልቅ ስኬት ነው፡፡ ወንድማችን ግን ይህንን አድርጐ አሳይቶናል፡፡









“የምግብ ዘይት ንግድ በጥቂት ኩባንያዎች ተይዟል” የሚል ውንጀላ የሚያዘወትረው መንግስት፣ “በዚህም ምክንያት ተጨማሪ ቁጥጥርና ጣልቃገብነት ያስፈልጋል” የሚል መከራከሪያ ያቀርብ ነበር።
አሁን ግን፣ ከደርዘን በላይ ኩባንያዎችን ከምግብ ዘይት ንግድ በማስወጣት፣ ለ4 ኩባንያዎች ብቻ ፈቀደ።
“በገዢው ፓርቲ የተቋቋሙ የንግድ ድርጅቶች፣ ከመንግስት አንዳችም ልዩ ጥቅም አያገኙም። መረጃ ካለ ግን አምጡ። ያለማመንታት እርምጃ እንወስዳለን” የሚል መከራከሪያ ያቀርብ ነበር።
በገዢው ፓርቲ የተቋቋሙት ድርጅቶች፣ ለበርካታ ኩባንያዎች በተከለከለው የዘይት ንግድ እንዲሰማሩ ልዩ ፈቃድ ተሰጥቷቸዋል።

     ባለፉት አምስት ዓመታት፣ የዋጋ ንረትን እከላከላለሁ በሚል ሰበብ የአገርን ገበያ በማተራመስ የንግድ ሚኒስቴርን የሚስተካከል መ.ቤት ያለ አይመስለኝም - በተለይ ከ2003 ዓ.ም ወዲህ።  ምናልባት መረጃው ከሌላችሁ፣ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር የሚደርስ የገንዘብ ኖት በገፍ የታተመበት ዓመት እንደሆነ ላስታውሳችሁ። በትክክለኛው አጠራር፣ “ኢንፍሌሽን” የሚባለውም ይሄው ነው - በባዶ የገንዘብ ኖት ማተም። የወርቅ ሳንቲም ላይ ተራ ብረት እየጨመሩ የውሸት ከማብዛት የተለየ አይደለም።
እንዲያውም፣ የድሮ መንግስታት ከሚጠቀሙባቸው “የኢንፍሌሽ” ዘዴዎች አንዱ ይሄው የብረዛ ዘዴ ነው። ሌላኛው “የኢንፍሌሽን” ዘዴ ደግሞ፣ የሳንቲሙን ስፋትና ውፍረት መቀነስ ነው። አንዱን ሳንቲም በቀጭኑ ለሁለት ሰንጥቆ ሁለት ሳንቲም እንደማተም ቁጠሩት።
እንዲህ በቀጭኑ ተባዝተው ወይም በብረት የተበርዘው የሚመጡ ሁለት ሳንቲሞች፣ ከኦሪጅናሉ አንድ የወርቅ ሳንቲም አይበልጡም። የውሸት ነው ቁጥራቸው የተጋነነው፤ ሳንቲሞቹን በማርከስ ነውና።
የብር ኖት አለቅጥ በገፍ ሲታተምም፣ ከዚህ የተለየ አይደለም። ገንዘብን በማርከስ ነው፣ ቁጥሩን የምናበረክተው። ገንዘብ ሲረክስ (ኢንፍሌት ሲደረግ) ደግሞ፣ ውሎ እያደረ የዋጋ ንረትን ያስከትላል። ለዚህም ነው፣ በ2003 ዓም በገፍ ከታተመው የብር ኖት ጎን ለጎን የሸቀጦች ዋጋ ከጣሪያ በላይ የተተኮሰው።
ሁሌም እንዲሁ ነው። የብር ኖት አለቅጥ ሲታተም፣ የዋጋ ንረት ይፈጠራል (ነጋዴዎች አንዳች የዋጋ ንረት አባዜ ድንገት ስለሚነሳባቸው አይደለም ዋጋ የሚንረው)። መንግስት ህትመቱን ረገብ ሲያደርግ ደግሞ፣ ባለፉት ሦስት አመታት እንደታየው የዋጋ ንረት ይረጋጋል (ነጋዴዎች በአንዳች ተዓምር ባሕሪያቸው ስለተቀየረ አይደለም)። እነዚህ ሁሉ፣ በሚስጥር የተያዙ ልዩ መረጃዎች አለመሆናቸውን ልብ በሉ። በብሔራዊ ባንክ አመታዊ የሂሳብ ሪፖርቶች ላይ የሰፈሩ መረጃዎች ናቸው።
እንዲያም ሆኖ፣ የዋጋ ንረት በተፈጠረ ቁጥር፣ የመንግስት ጥፋት የሚላከከው በነጋዴዎች ላይ ነው። በ2003ም ከዚህ የተለየ ነገር አልታየም። “አጭበርባሪ ስግብግብ ነጋዴዎች!” እየተባለ፣ ቀን ከሌት ከሚዥጎደጎደው ውንጀላ ጋር፤ የንግድ ሚኒስቴር አዳዲስ የቁጥጥር መመሪያዎችን ያወርደው ጀመር። ደርግ ተመልሶ የመጣ ነበር የሚመስለው።
በየደቂቃው በሚሊዮኖች ድርድርና ግብይት እየተቃኘ እየተስተካከለ የሚፈጠረውን የሸቀጦች ዋጋ፣ በአንድ መስሪያ ቤት ባለስልጣናት ግምት እና በአንድ መመሪያ አሳስሮ ለማንበርከክ መሞከር... እንዴት የጤና ሊሆን ይችላል? የደርግ የገበያ ቁጥጥር ምን እንዳስከተለኮ በተግባር ታይቷል። ያንኑን ተመልሶ መድገም፣ ትርጉሙ ምንድነው?
ለገላ ሳሙና አንድ የዋጋ ተመን፣ ለልብስ ሳሙና አንድ የዋጋ ተመን... ገበያ ውስጥ ላለው የሳሙና አይነት ሁሉ ሁለት የዋጋ ተመን ሲወጣለት አስቡት። የተወሰኑ ቢሮክራቶች የሚሊዮን ሰዎችን ሕይወትና ግብይት ለመቆጣጠር ሲሞክሩ፣ እንዲህ አይነት እብደት ነው የሚፈጠረው።
“መሰረታዊ ሸቀጦች” በሚል ዝርዝር ውስጥ በቀዳሚነት የዋጋ ተመን ከወጣላቸው ምርቶች መካከል፣ ለስላሳ መጠጥና ቢራ መካተታቸውንም አስታውሱ። እና... ለስላሳና ቢራ፣ ለአብዛኛው ሰው እጅግ አሳሳቢ የሆኑ “መሰረታዊ ሸቀጦች” ናቸው ብሎ ማወጅ የጤንነት ነው?
ፓልም የምግብ ዘይት፣ የጥራት ደረጃው ምንም ይሁን ምን፣ የሽያጭ ቦታው ርቀት የትም ይሁን የት፣ በሊትር የ16 ብር ከሃምሳ ሳንቲም የዋጋ ተመን ከወጣለት በኋላ ምን እንደተፈጠረስ ትዝ ይላችኋል? የንግድ ሚኒስቴር ሰዎች፣ ነጋዴዎች አይደሉም። ለካ፣ በዚያን ጊዜ አብዛኛው የምግብ ዘይት፣ ከኢንዶኔዢያ በሊትር ከሃያ ብር በላይ እየተገዛ ነው ከውጭ የሚመጣው። ቢሮክራሮቹ ያወጡለት የዋጋ ተመን ግን 16.50 ነው። እንዴት ነው ነገሩ? መቼም ኢንዶኔዢያ ሄደው፣ የፓልም ምርት ኮታና የዘይት ዋጋ ተመን ማወጅ አይችሉም። ታዲያ፣ የንግድ ሚኒስቴር ባለስልጣናት፣ ምን አይተው ነው ለኢትዮጵያ የምግብ ዘይት ገበያ የዋጋ ተመን ያወጡት? ከጥቂት የግርግር ቀናት በኋላ፣ በሊትር 24 ብር ይሁን ብለው ሌላ መመሪያ አወጡ።
ግን፣ ምን ዋጋ አለው? የሸቀጦች ምርትና የሰዎች የምግብ ምርጫ በመመሪያ የሚወሰን አይደለም። የኢንዶኔዢያ የፓልም አዝመራ ከፍና ዝቅ ይላል። የኢትዮጵያ የኑግ ምርትና የቅቤ አቅርቦትም በቢሮክራቶች ኮታ የሚወሰን አይደለም። የውጭ ምንዛሬ በአለም ደረጃ እንዲሁም እዚሁ አገር ከጊዜ ወደ ጊዜ ይለዋወጣል። እነዚህንና ሌሎች በርካታ ነገሮችን በማገናዘብ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በየደቂቃው በሚያካሂዱት እልፍ ግብይት አማካኝነት ነው የፓልም ዘይት ዋጋ የሚወሰነው። አንዱ ተነስቶ በዘፈቀ፣ የገበያ ዋጋ ልወስን ማለት አይችልም። በጉልበት ተመን ሲያወጣም፣ ገበያንና ኢኮኖሚን ከማናጋት ያለፈ ውጤት የለውም።
የንግድ ሚኒስቴር በዋጋ ተመን የአገሬውን ገበያ ለወራት ሲያምስ ቆይቶ ነው፤ አብዛኞቹን የዋጋ ተመኖች እንዲሰረዙ የተደረገው። ያልተሰረዙ ግን አሉ። የየትኞቹ ሸቀጦች የዋጋ ተመን እንዳልተሰረዘ ለመገመት አይከብድም። ለመገመት ከፈለጋችሁ፣ “ላለፉት ሦስት አመታት ብዙ ሰው የተቸገረባቸው ሸቀጦች የትኞቹ ናቸው?” ብላችሁ ጠይቁ። አዎ፤ ስኳር፣ ዳቦ እና የምግብ ዘይት ... እነዚህ ላይ የዋጋ ቁጥጥሩ አልተሰረዘም። የሦስቱ ሸቀጦች ገበያ ሊረጋጋ ያልቻለው ለምንድነው? የስኳር፣ የዳቦ ስንዴ እና የምግብ ዘይት የጅምላ ንግድ ሙሉ ለሙሉ በመንግስት ቁጥጥር ስለሆነ ነዋ።
“ደግነቱ”፣ ገበያውን ለአራት አመታት ሲያናጋ ከቆየ በኋላ፤ በቅርቡ በምግብ ዘይት ገበያ የግል ኩባንያዎችን ማስገባት ያስፈልጋል ተብሎ ተወስኗል። በእርግጥ፣ አመታትን መጠበቅ አያስፈልግም ነበር። ገበያን መቆጣጠር፣ ችግር ከማባባስ ውጭ ሌላ ውጤት እንደሌለው ለመገንዘብ፣ የግድ እልፍ ጊዜ በእልፍ ቦታ እየደጋገምን ብዙ የቀውስ አይነት ማየት አለብን? ደርግ፣ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ያንኮታኮተው በገበያ ቁጥጥር ነው። በአፍሪካና በአውሮፓ፣ በኤሽያና በደቡብ አሜሪካ ከመቶ በላይ አገራት ለበርካታ አመታት ሲሞክሩትና ኢኮኖሚያቸውን ሲያቃውሱ አይተናል። እዚሁ አገራችን ውስጥ በ2003 ዓ.ም የሙዝና የብርቱኳን፣ ቢራና የለስላሳ፣ የፓስታና የሳሙና ምርቶች ላይ በወጣው የዋጋ ተመን ገበያው ሲናጋ ተመልክተናል። “በገበያ ቁጥጥር አማካኝነት ሌላ ውጤት እናገኛለን” ብለን ራሳችንን የምናታልለው እስከ መቼ ነው? በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ፣ “በተመሳሳይ ድርጊት ከወትሮው የተለየ ውጤት መጠበቅ”፣ የጤና አይደለማ።
ለማንኛውም ግን፣ ከአራት አመታት በኋላም ቢሆን፣ የምግብ ዘይት ንግድን በመንግስት ቁጥጥር ስር ማድረግ እንደማይበጅ ተገንዝቦ፣ ስህተትን ለማስተካከል መታሰቡ መጥፎ አይደለም። በዚያው እብደት ከመቀጠል፣ ዘግይቶም ቢሆን ለማስተካከል መሞከር ይሻላል።
አሳዛኙ ነገር፣ የማስተካከያ ሙከራው ጎደሎና የተዛባ ስለሆነ፣ ለዜጎች የሚያስገኘው ጥቅም የዚያኑ ያህል ትንሽ ይሆናል። ለመንግስትና ለኢህአዴግማ፣ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል። ከገበያ ቁጥጥር ጋር ተያይዞ በተስተዋለው የመዝረክረክ ዝንባሌ ሳቢያ የተሸረሸረውን ተአማኒነት ይበልጥኑን ያመናምንባቸዋል። ለምን?
አንደኛ፣ የምግብ ዘይት ንግድን ለአራት የግል ኩባንያዎች ብቻ በመፍቀድ ሌሎችን ከልክሏል። ሁለተኛ፣ በኢህአዴግ ገንዘብ ለተቋቋሙ አራት የንግድ ድርጅቶች ልዩ ፈቃድ ሰጥቷቸዋል።

እንግዲህ አስታውሱ። መንግስት በ2003 ዓም “የምግብ ዘይት ንግድ ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር ያስፈልጋል” ብሎ ለምን እንደወሰነ፣ ዋነኛ ምክንያቱን (ዋነኛ ሰበቡን) በግልፅ እንደነገረን አትርሱ። “ጥቂት ኩባንያዎች የዘይት ገበያውን ተቆጣጥረውታል” የሚል ነበር ሰበቡ። ከውጭ አገር የፓልም ዘይት የሚያስመጡ የግል ኩባንያዎች፣ ሃያ ወይም ሰላሳ ብቻ እንደሆኑ ገልፆልን ነበር። አሁንስ?
አራት ግል ኩባንያዎች ብቻ ፓልም ዘይት እያስመጡ እንዲነግዱ ሲፈቀድላቸው፣ ሌሎች ከደርዘን በላይ የሚሆኑ ኩባንያዎች ግን ተከልክለዋል። “ጥቂት ኩባንያዎች ንግዱን ተቆጣጥረውታል” በማለት የቁጥጥር ሰበብ የሚያቀርብ መንግስት፤ “ከሃያ ኩባንያዎች ይልቅ አራት ኩባንያዎች ብቻ ቢነግዱ ይሻላል” ብሎ ሲወስን ተአማኒነትን ያስገኛል? ሊያስገኝ አይችልም። ተአማኒነትን ይሸረሽራል እንጂ።
በእርግጥ፣ አራቱ የግል ኩባንያዎች፣ ከውጭ የፓልም ዘይት እንዲያስመጡ የተፈቀደላቸው እዚሁ አገር የዘይት ፋብሪካ እየከፈቱ በመሆናቸው ነው የሚል ምክንያት ቀርቧል (እንዲህ አይነት የፈቃድ አሰጣጥ ህግም ሆነ መመሪያ ባይኖርም)። ግን፣ እሺ ይሁን። ታዲያ፣ በገዢው ፓርቲ ገንዘብ (በኢንዶውመንት) የተቋቋሙት ሌሎች አራት የንግድ ድርጅቶችስ፣ የምግብ ዘይት እያስመጡ እንዲነግዱ ለምን ተፈቀደላቸው? የዘይት ፋብሪካ እያቋቋሙ ስለሆነ አይደለም። እናስ ለምን?  
ከኢህአዴግ በተሰጠ ገንዘብ የተቋቋሙት የንግድ ድርጅቶች፣ ገና ከመነሻቸው ጀምሮ ላለፉት ሃያ አመታት አከራካሪ ሆነው የቆዩ ድርጅቶች ናቸው። መንግስት በአድልዎ ልዩ ጥቅም ይሰጣቸዋል በማለት የንግድ ምክርቤት በተደጋጋሚ ያቀረበውን አቤቱታ መጥቀስ ይቻላል። የአለም ባንክም በየጊዜው በሚያወጣቸው ሪፖርቶች፣ በፖርቲ የተቋቋሙት የንግድ ድርጅቶች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከሌሎች የግል ኩባንያዎች የተለየ ጥቅም ማግኘታቸው አይቀርም በማለት በተደጋጋሚ ተችቷል። የመንግስት ምላሽ፣ ሁልጊዜም ተመሳሳይ ነው - “በኢንዶውመንት የተቋቋሙት ድርጅቶች፣ በአድልዎ የሚያገኙት አንዳች ልዩ ጥቅም የለም። ልዩ ጥቅም እንደሚያገኙ የሚያሳይ መረጃ ካመጣችሁ ያለማመንታት እርምጃ እንወስዳለን” በማለት ይከራከራል። በእርግጥም፣ መከራከሪያዋ ለመንግስት ተአማኒነትን ባያተርፍለትም፣ በቀላሉ ውድቅ ለማድረግ አስቸጋሪ በመሆኗ ተአማኒነትን ሙሉ ለሙሉ ከማጣት አግዛዋለች። ይህችን መከራከሪያ ላለማጣት በእጅጉ ሲጠነቀቅ መቆየቱም አይገርምም።
አሁን ግን፣ መጠንቀቅ ይቅርና ነገሮችን ለመሸፋፈን የማይሞክርበት ደረጃ ላይ የደረሰ ይመስላል - ነገሮች ወደዚህና ወደዚያ እየተዝረከረኩ ነዋ። ይሄውና በገዢው ፓርቲ ገንዘብ የተቋቋሙት የንግድ ድርጅቶች፣ ለበርካታ የግል ኩባንያዎች በተከለከለው የምግብ ዘይት ንግድ ውስጥ እንዲገቡ ልዩ ፈቃድ (ልዩ ጥቅም) ተሰጥቷቸዋል - በግላጭ። ይሄ ጠንቃቃነትን አያሳይም።

“በኢትዮጵያ ስላለው የመብት ረገጣ 90 ሚሊዮን ህዝብ ምስክር ነው”
- ለእድገታችን አሜካ ምስክር ሆነችልን ማለት ውጤት አያመጣም - ዶ/ር መረራ

    በአለማቀፍ ታላላቅ የሚዲያ አውታሮች መነጋገሪያ ሆኖ የዘለቀው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ኢትዮጵያን የመጐብኘት ውጥን አሜሪካ አምባገነን መንግስታትን ከመደገፍ የመነጨ በመሆኑ እምብዛም ትኩረት የሚሠጠው ጉዳይ አይደለም ብለዋል - የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች፡፡
ዶ/ር መራራ ጉዲና
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሣይንስ መምህር እና የመድረክ የፖለቲካ ማህበር አመራር ዶ/ር መረራ ጉዲና የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት ዋነኛ ትኩረቱ የሽብር ጉዳይ ነው ይላሉ፡፡
የአሜሪካ ትልቁ ትግል ሽብርተኝነትን ማሸነፍ በመሆኑ ኢትዮጵያ ለአሜሪካ ፀረ - ሽብር ፖሊሲ አጋር ነች መባሉ ለጉብኝቱ ዋጋ አለው የሚሉት ዶ/ር መረራ፣ በዚያው ልክ አሜሪካ አምባገነኖችን የምትደግፍም ሃገር መሆኗን በምሳሌ አስደግፎ ማስረዳት ይቻላል ይላሉ፡፡ በቀዝቃዛው ጦርነት ጊዜ “የኛ ወዳጅ ነው” እያሉ የአፍሪካ ቁጥር አንድ አምባገነን የነበረውን  ሞቦቱ ሴሴኮን እና ሌሎች ነፍሰ ገዳይ የነበሩ መሪዎችን ለራሷ ጥቅም ስትል ስትደግፍ ኖራለች፤ የፕሬዚዳንቱ ጉብኝትም የተለየ አንድምታ የለውም፤ የዚሁ ፖሊሲም ውጤት ነው ብለዋል ምሁሩ - ዶ/ር መረራ። “የኔ አሽከሮች እስከሆኑ ድረስ ምንም ቢያደርጉ ሆዴ አይጨክንባቸውም” የሚል ፖሊሲ ሃገሪቱ አላት” ያሉት ዶ/ር መረራ “እናሸንፋለን ብለው የገቡበት የሽብር ትግል አቅጣጫውን ቀይሮ እየሰፋ መምጣቱ ለጭንቀት ዳርጓቸው ጉዳይ አስፈፃሚ ሃገራትን እንዲንከባከቡ አስገድዷቸዋል” ብለዋል፡፡
“ዲሞክራሲ እንደሸቀጥ እቃ ከውጪ ተገዝቶ የሚመጣና የሚሸጥ አይደለም የሚሉት ዶ/ሩ፤ “የኢትዮጵያ ህዝብ ከሚያደርገው ትግል የሚመጣ በመሆኑ አንድ የአሜሪካ መሪ ዲሞክራሲያዊ ያልሆነ ሀገርን ስለጐበኘ የትግሉ ተዋናዮች ተስፋ መቁረጥ የለባቸውም ሲሉም አሳስበዋል፡፡
በአሜሪካ ይደግፍ የነበረው የአፄ ኃይለሥላሴ ስርአትም ሆነ በሶቪየቶች ይደገፍ የነበረው የደርግ ስርአት መውደቁን ያስታወሱት ዶ/ር መረራ፤ ይሄም ስርአት ሃቀኛ ዲሞክራሲ ስለማስፈኑ የኦባማ ጉብኝት ማረጋገጫ አይሆንም፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ትግልንም አያዛንፈውም ብለዋል፡፡
“ኦባማ ኢትዮጵያን በዚህ ሁኔታ መጐብኘት ለአሜሪካ ህዝብ አሣፋሪ ነው” ያሉት ዶ/ር መረራ በአንፃሩ የኢትዮጵያን ህዝብ ትግል የሚገታው አይሆንም ብለዋል፡፡ ኦባማ ወደ ስልጣን ሲመጣ አምባገነኖች ቦታ አይኖራቸውም እያለ ስለዲሞክራሲ የሚዘምር የነበረና የወጣቶችን ቀልብ መግዛት የቻለ ነበር የሚሉት ዶ/ሩ በመጨረሻ በዚህ ደረጃ መውረዱ ቃሉን እንደበላ ነው የሚያረጋግጠው ብለዋል፡፡
የመላ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት
የመላ ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፕሬዚዳንት አቶ አበባው መሀሪ በበኩላቸው፤ ፕሬዚዳንቱ የሚመጣበት ጉዳይ ወሳኝነት እንዳለው ጠቅሰው የኢትዮጵያ መንግስት እየፈፀመ ያለውን የዲሞክራሲያዊ መብቶችና ሰብአዊ መብት ጥሰቶችን እንዲያርም የሚያሣስቡ ከሆነ ጉብኝቱ አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል፤ ዝም ብሎ በፀረ ሽብር ጉዳይ ላይ ተወያይቶ የሚመለሱ ከሆነ ትክክል አይሆንም ብለዋል፡፡
ወሳኙ ፕሬዚዳንቱ መጥቶ ምን አድርጐ ነው የሚሄደው የሚለው ጥያቄ ነው፤ የሚሉት አቶ አበባው፤ የሃገሪቱን እድገት አድንቆና ሽብር ላይ ዘክሮ የሚመለስ ከሆነ መምጣቱ ውጤታማ አይሆንም ብለዋል፡፡
ሠማያዊ ፓርቲ
የሠማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊው ዮናታን ተስፋዬ በበኩሉ፤ “የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ወደ ኢትዮጵያ መምጣት በፓርቲው በኩል ብዙም ትኩረት የሚሠጠው አይደለም” ብሏል፡፡ “ድሮም አሜሪካ አምባገነኖችን ትረዳ ነበር አሁንም እየረዳች ነው” ያለው ዮናታን፤ “በኢትዮጵያ ውስጥ ላለው አፈናና ጭቆናም አንደኛዋ ተባባሪ አሜሪካ ስለሆነች ህዝቡም ያን ያህል ትኩረት የሚሰጠው አይመስለኝም” ብሏል፡፡
ኢዴፓ፣ መኢአድ እና ኢራፓ
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጋራ ጉዳዮች ላይ አብረው ለመስራት ተስማምተናል ያሉት ኢዴፓ፣ መኢአድ እና ኢራፓ በበኩላቸው፡- ፕሬዚዳንቱን የማግኘት የማነጋገር አድሉ ከገጠመን በሰብአዊ መብት ጥሰት እና ዲሞክራሲያዊ ስርአትን ባለማስፈኗ የምትታማን ሃገር ለመጎብኘት ለምን ፈለጉ የሚለውን እንጠይቃቸዋለን ብለዋል፡፡
የአሜሪካው 44ኛ ፕሬዚዳንት ባራክ ሁሴን ኦባማ በኢትዮ-አሜሪካ የ112 አመታት የዲፕሊማሲ ታሪክ ውስጥ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ማቀዳቸው መነጋገሪያ ሆኖ የከረመ ሲሆን ዋሽንግተን ፖስት እና ዘ ጋርዲያን ጋዜጦችን እቅዱን ክፉበኛ አብጠልጥለውታል፡፡

Published in ዜና

የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ መቀመጫ የኾነችው የቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ፥ ጥፋቶች ታርመው ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው አሰራር እንዳይሰፍን በሚሹ ጥቂት የአስተዳደር ሰራተኞች፣ በህይወት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር ከአድማ ያልተናነሰ እንቅስቃሴ እየተደረገበት መኾኑን አስታወቀ፡፡ የመልካም አስተዳደር ጅምሩን ከፍጻሜ ለማድረስ የቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ የአስተዳደር ክፍሎች እገዛ እንዲያደርጉለትም ጠይቋል፡፡
ለብክነት፣ ለዘረፋ እና ለሙስና ከተመቻቸ አሰራር እንዲሁም በገዳሟ ቀደም ሲል ከመልካም አስተዳደር ዕጦት የተነሳ የተከሰቱ ጥፋቶችን ለማረም ልዩ ልዩ መመሪያዎችንና የውስጥ ደንብ ረቂቆችን ማዘጋጀቱን ሰበካ ጉባኤው ለሀገረ ስብከቱ የዋና ሥራ አስኪያጅ ጽ/ቤት ባቀረበው ሪፖርት ገልጿል፡፡ ይኹንና ለቁጥጥር የሚያመች ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለበትን አሰራር ለማስቀጠልና ለማስፈጸም እንዳይቻል ጥቂት የአስተዳደር ሰራተኞች ማኅበረ ካህናቱን በመከፋፈል፣ “ከሰበካ ጉባኤው ጋር ተባብራችኋል” በሚል ከሥራና ከደመወዝ በማገድ፣ በማስጠንቀቂያዎች በማሸማቀቅ፣ መረጃዎችን በማዛባት የሚፈጥሩት ግጭት ኹኔታውን አስቸጋሪ አድርጎብኛል ብሏል፡፡
መመሪያዎቹ እና የውስጥ ደንቡ “ቀድሞ ሲዘርፉበት የነበረውን አካሄድ የሚያስቀር እና አለአግባብ የሚያካብቱትን ጥቅም የሚያስቆም ነው” ያለው ሰበካ ጉባኤው፤ ለህይወት አስጊ ባላቸው ተፅዕኖዎች ሳቢያ በገዳሟ ጽ/ቤት ተገኝቶ በሰላማዊ መንገድ ስራዎቹን ለማከናወንና ሐላፊነቱን ለመወጣት ከማይቻልበት ደረጃ መድረሱን በሪፖርቱ አስታውቋል፡፡  
እንደ ሰበካ ጉባኤው ገለጻ፥ ቃለ ዐዋዲውን መሰረት አደርጎ ለቤተ ክርስቲያን በሚበጅ መልኩ ያዘጋጃቸው የሰው ኃይል አስተዳደር፣ የፋይናንስ፣ የንብረት እና የግዥ መመሪያዎች በጽ/ቤቱ ልዩ ትርጉም እየተሰጣቸው በመደበኛ ስብሰባ ላይ እንኳን አስተያየት እንዳይሰነዘርባቸው  ዕንቅፋት ተፈጥሯል፤ ማኅበረ ካህናትና ሰራተኞች ገንዘብንና ንብረትን የሚቆጣጠር አካል ቢመርጡም፣ የቆጠራ ሥርዓትን አስመልክቶ ከወራት በፊት በሀገረ ስብከቱ የተላከው መመሪያ ለኮሚቴው ቀርቦ ወደ ተግባር ሳይተረጎም በቢሮ ተሸሽጎ እንደተቀመጠ ነው፤ የቆጠራ ደንቡንና መመሪያውን ከማስፈጸም ይልቅ ከመመሪያው የተነሳ ህገ ወጥ ጥቅም የቀረባቸውን ግለሰቦች በማነሣሣት ለተቃውሞ እንዲቆሙ ይደረጋል፡፡ያለፉት ስድስት ዓመታት የገንዘብ እና ንብረት እንቅስቃሴ በገለልተኛ ኦዲተር እንዲመረመር በፓትርያርኩ ቢታዘዝም “ከቃለ ዐዋዲው ውጭ ነው” በማለት ሒደቱ በሒሳብ ክፍሉ እና በጽ/ቤቱ ተጓትቷል፤ ይልቁንም የሒሳብ ፍተሻ ሒደቱ እና የሰበካ ጉባኤው የተሻሻሉ አሰራሮች ትግበራ ከሚያስከትሉት ተጠያቂነት ለማምለጥ የአስተዳደር ሐላፊዎቹ፣ “ሰበካው እየረበሸን ነው፤ የደመወዝና ጥቅማ ጥቅሞች ዕድገት እንዳናደርግላችሁ ዕንቅፋት ሆኖብናል፤ ከእኛ ጎን ከቆማችሁ ቢሮ አካባቢ እንመድባችኋለን፤ ወዘተ…” በማለት ከማኅበረ ካህናቱ ጋር ማጋጨትና መከፋፈል ስራዬ ብለው ከመያዛቸውም በላይ በዓመት ፈቃድ ሰበብ ከቢሯቸው ይሸሻሉ፡፡
በግንቦት ወር መጨረሻ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሥራ አስኪያጅ ጽ/ቤት የተላከው ይኸው የሰበካ ጉባኤው ሪፖርት፤ ከተደጋጋሚ ጥያቄ በኋላ በቁጥጥር ክፍሉና በሒሳብ ክፍሉ በቀረቡ የገዳሟ የፋይናንስ አቋም ማሳያ ሪፖርቶች ላይ የተካሔደው ንጽጽራዊ ግምገማ፤ ገዳሟ በ2006 ዓ.ም ከየካቲት እስከ ነሐሴ ባሉት ሰባት ወራት ብቻ ከብር 1.5 ሚሊዮን በላይ ተመዝብራለች፤ በዚህ ከፍተኛ የገንዘብ ጉድለት እንቅስቃሴ ሂሳብ ሹሙ፣ ገንዘብ ያዡ፣ ፀሐፊው፣ ቁጥጥሩና የቀድሞው አስተዳዳሪ ተጠያቂዎች እንደሆኑ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም ከንዋያተ ቅድሳት ወርኀዊ ሽያጭ ጋር በተያያዘ ገዳሟ ከታህሣሥ ወር 2007 ዓ.ም በፊት ባሉት ጊዜያት በየወሩ በአማካይ ከብር 100ሺህ በላይ ስትመዘበር መቆየቷን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ለዚህም በዋናነት ተጠያቂው የንብረት ክፍል ሐላፊው እንደሆኑ ገልጿል፡፡
በገዳሟ በገንዘብ ዝውውርና በንብረት አጠባበቅ የሚታየው ከፍተኛ የአሠሰራር ድክመትና የሠራተኞች የአቅም ማነስ የመግባባት ችግር ከመፍጠሩም ባሻገር በልዩ ልዩ የአስተዳደር ክፍሎች ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን ሪፖርቱ አክሎ አብራርቷል፡፡
የገዳሟ ጸሐፊ መጋቤ ስብሐት ኃ/ጊዮርጊስ ዕዝራ በበኩላቸው፣ ሪፖርቱ እንዳልደረሳቸው ቢናገሩም የተጠቀሰውን የገንዘብ ጉድለት ጨምሮ የሪፖርቱ ይዘት “ሙሉ በሙሉ ውሸት ነው” በሚል አስተባብለዋል፤ ተጨማሪ ጥያቄዎችንም በስልክ ለመመለስ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡  

Published in ዜና

የጆሊ ጁስ አምራች የሆነው ቴስቲ ፉድስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግ. ኩባንያ፤ በጥራት የስራ አመራር ብቃት ጥራቶችን አሟልቶ አለማቀፉን የISO 9001/2008 ሰርተፊኬት ተሸላሚ መሆኑን የኩባንያው ሃላፊዎች ገለጹባ የተለያዩ የሚበጠበጡ የዱቄት ጣፋጭ መጠጦችንና ቴስቲ ስናክን የሚያመርተው ኩባንያው፤ የአለማቀፉ ጥራት ተሸላሚ መሆኑ፣ ምርቶቹን ወደ አለማቀፍ ገበያ ይዞ እንዲቀርብና ተቀባይነት እንዲያገኝ ይረዳዋል ተብሏል፡፡ ከ8 ዓመት በፊት የተቋቋመው ኩባንያው፤ታዋቂውን የጆሊ ጁስ መጠጥ ጨምሮ የተለያዩ የፍራፍሬ ጣዕም ያላቸውን በውሃ ተበጥብጠው የሚጠጡ ፍሌቨሮች የሚያመርት ሲሆን ደረቅ ቴስቲ ስናክ በማምረትም ከሃገር ውስጥ በተጨማሪ ለውጪ ገበያ እንደሚያቀርብ ተጠቁሟል፡፡  
ኩባንያው ለወደፊት የምርቶቹን የጥራት ደረጃ ጠብቆ በኢትዮጵያ ያለውን የገበያ አድማስ ለማስፋት እንደሚተጋ የስራ ኃላፊዎቹ ገልፀዋል፡፡

Published in ዜና

ከውጭ የሚገባውን የቢራ ገብስ ምርት እስከ መጪዎቹ ሁለት አመታት ሙሉ በሙሉ ለማስቀረት ታስቦ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን በመተግበር ላይ በሚገኘው ፕሮጀክት ውጤታማ የሆኑ አርሶ አደሮች ተሸለሙ፡፡
ክሪኤት የተባለውና ላለፉት ሁለት አመታት በዞኑ ሲተገበር የቆየው ፕሮጀክቱ፤ የተሻሻለና ጥራት ያለው የቢራ ገብስ ምርት ማምረት እንዲቻል ለአርሶ አደሮች እገዛ የሚሰጥ ነው፡፡
በግብርና ሚኒስቴርና በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ድጋፍ ሰጪነት የተዘረጋውን ፕሮጀክት፤ የኔዘርላንድ መንግስትና ሔኒከን ቢራ ፋብሪካ በገንዘብ እንደሚደግፉት ታውቋል፡፡
የሔኒከን ኩባንያ የጥሬ እቃ ማበልፀግ ኃላፊ አቶ ታረቀኝ ጋሩምሳ እንደተናገሩት፤ ባለፉት ሁለት አመታት በዚህ ፕሮጀክት 10ሺ 200 አርሶ አደሮች እንደሆኑ የተደረገ ሲሆን፤ በቀጣዮቹ ሁለት አመታት ተጨማሪ 10ሺ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ ውጤታማ ስራ ለማከናወን እንቅስቃሴው ቀጥሏል።
በፕሮጀክቱ ተሳትፈው ውጤታማ እንቅስቃሴ ያከናወኑ ማህበራትና አርሶ አደሮች ሰሞኑን በአርሲ በርሔ ኢ ሆቴል የግብርና መሳሪያዎችና ሌሎች ማበረታቻዎች እንተበረከተላቸው ለማወቅ ተችሏል።
የሔኒከን ኢትዮጵያ ኮርፖሬት ግንኙነት ኃላፊ ወ/ሮ ሠራዊት በዛብህ በሽልማት አሰጣጥ ሥነ ሥርዓቱ ወቅት እንደገለፁት፤ በዚህ ፕሮጀክት ተሳትፈው ውጤታማ የሆኑ አርሶአደሮችን መሸለም ያስፈለገው ለማመስገንና የበለጠ እንዲተጉ ለማበረታታት ነው፡፡
ፕሮጀክቱ ለአርሶአደሮቹ የሙያ፣ የገንዘብ እንዲሁም የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ጥራት ያለው የገብስ ምርት እንዲያመርቱ የሚያግዝ እንደሆነም ሃላፊው ጠቁመዋል፡፡ በፕሮጀክቱ ዕቅድ መሠረት፤ ኢትዮጵያ በ2017 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) 20ሺ ሜትሪክ ቶን የቢራ ገብስ በማምረት ከውጭ የምታስገባውን ምርት ታስቀራለች ተብሏል።

Published in ዜና

    በህገወጥ የሰዎች ዝውውርና ስደተኞችን በህገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል ላይ ከፍተኛ ቅጣት የሚያስጥል አዲስ ረቂቅ ህግ ወጣ፡፡
ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበውና ትናንት በምክር ቤቱ ውይይት የተደረገበት ረቂቅ አዋጅ፤ በወንጀለኞች ላይ እስከ ሞት የሚደርስ ቅጣት የሚያስቀጣ አንቀፅ ተካትቶበታል፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰና ስር እየሰደደ ዜጎችን ለአስከፊ የሰብአዊ መብቶች ጥሰትና እንግልት እየዳረገ በመሆኑ በወንጀለኞች ላይ ለጥፋታቸው ተመጣጣኝ የሆነ ቅጣት ለመጣል የሚያስችል ህግ ማውጣት በማስፈለጉ ረቂቅ ህጉ መዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡
ረቂቅ ህጉ በማንኛውም ህገወጥ መንገድ ስደተኞችን ወደአገር ውስጥ ማስገባትም ሆነ ከአገሪቱ ግዛት ማስወጣት ከ15-20 ዓመት ለሚደርስ ፅኑ እስራትና ከ150ሺ - 300ሺ ብር ለሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ይዳርጋል፡፡ ድርጊቱ የተፈጸመው በስፋትና በበርካታ ሰዎች ላይ ከሆነ አሊያም የወንጀል ድርጊቱ በተጎጂው ላይ ከፍተኛ የአካል ጉዳት ወይም ሞት ያስከተለ ቅጣቱ የዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት ወይም ሞት ሊሆን ይችላል፡፡
ማንኛውም ሰው ስደተኞችን በህገወጥ መንገድ ድንበር በማሻገር ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ለማስገባት ወይም ከኢትዮጵያ ግዛት ለማስወጣት የተጭበረበረ ወይም ሀሰተኛ መታወቂያ ካርድና የጉዞ ሰነዶችን ካዘጋጀ፣ ይዞ ከተገኘ፣ ካቀረበ ወይም ካስተላለፈ ከ10 ዓመት በማያንስ ከ20 ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራትና እስከ 200ሺ ብር በሚደርስ የገንዘብ ቅጣት ይቀጣል፡፡
በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ወይም ስደተኞችን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር በማሻገር ወንጀል ተጠርጥሮ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋለ ተጠርጣሪ እስከ አራት ወራት የሚደርስ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ሊጠየቅበት እንደሚችል የሚደነግገው ረቂቅ ህጉ፤ በወንጀሉ ላይ የሚቀርቡ ክሶች ወይም ቅጣቶች በይርጋ እንደማይታገዱም ያዝዛል፡፡
የህገወጥ ስደቱ ተጎጂ የሆኑ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል ፈንድ መቋቋሙም በረቂቅ ህጉ ላይ ተጠቅሷል፡፡
ይህንኑ ወንጀል ለመቆጣጠርና ለመከላከል የሚያስችልና የተጎጂዎችን መልስ ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት የሚደግፍና ተጠሪነቱ ለብሔራዊ ኮሚቴ የሆነ የፀረ ህገ ወጥ ሰዎች ዝውውርና ስደተኞችን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር የጋራ የግብረ ኃይል መቋቋም በረቂቅ አዋጁ ላይ ተገልጿል፡፡
ፍርድ ቤት በጥፋተኛው ላይ ከሚወስነው ቅጣትና መቀጫ በተጨማሪ ለተጎጂው ወይም በተጎጂው ስም ወጭ ላወጡ ሌሎች ሰዎች ወይም ድርጅቶች ካሳ እንዲከፍል ሊወስን ይችላል ያለው ረቂቅ ህጉ፤ ካሳው እንደነገሩ ለህገወጥ ደላላ ከከፈለው ገንዘብ፣ በወንጀል ድርጊቱ ምክንያት ተጎጂው ካጣው ወይም ህገወጥ ደላላው ካገኘው ጥቅም መጠን ያነሰ መሆን የለበትም፡፡
ተጐጂው ከወንጀል ፈፃሚው  ካሳ ማግኘት ካልቻለ የማካካሻ ክፍያ ከፈንዱ እንዲከፈለው ይደረጋል የሚለው ረቂቅ ህጉ፤ ይህም የሚሆነው ኢትዮጵያዊ ዜግነት ላላቸው ተጎጂዎች ብቻ መሆኑን ይጠቁማል፡፡

Published in ዜና

ኢትዮጵያ በነፍስ ወከፍ ገቢ ከ213 አገራት 203ኛ ሆናለች
- መንግስት የነፍስ ወከፍ ገቢያችን ከ550-700 ዶላር ደርሷል ይላል
- ሞናኮ በ100 ሺህ ዶላር ስትመራ፣ ማላዊ በ250 ዶላር መጨረሻ ላይ ትገኛለች
           በየአመቱ ሃምሌ ወር መጀመሪያ ላይ የዓለማችንን አገራት ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ይፋ የሚያደርገው የአለም ባንክ፣ ባለፈው የፈረንጆች አመት የኢትዮጵያ አመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ 550 ዶላር እንደነበር ገለፀ፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ፤ አመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢያችን ከ550-700 ዶላር ደርሷል ማለቱ ይታወቃል፡፡የዓለም ባንክ ከትናንት በስቲያ ያወጣው የአለማችን አገራት የኢኮኖሚ ሁኔታ መረጃ እንደሚያሳየው፣ ኢትዮጵያ በአመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ ከዓለማችን 213 አገራት 203ኛ ደረጃን ይዛለች፡፡
የባንኩ ያለፈው ዓመት የአገራት አመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ መረጃ እንደሚያሳየው፤ 10 የአለማችን አገራት፣ በ2013 ከነበራቸው የነፍስ ወከፍ ገቢ ጭማሪ ያሳዩ ሲሆን፣ ካላደጉ የአለማችን አገራት መካከል ባንግላዴሽ፣ ኬንያ፣ ማያንማር እና ታጂኪስታን የነፍስ ወከፍ ገቢያቸውን በማሻሻል ወደ አነስተኛ መካከለኛ ገቢ አገራት ሲቀላቀሉ፣ ደቡብ ሱዳን በበኩሏ፤ የነፍስ ወከፍ ገቢዋ በመቀነሱ ከዝቅተኛ ገቢ አገራት ጋር ተቀላቅላለች ብሏል የአለም ባንክ፡፡ሞንጎሊያና ፓራጓይ በ2013 ከነበሩበት አነስተኛ መካከለኛ ገቢ፣ ዘንድሮ ወደ ከፍተኛ መካከለኛ ገቢ አገራት ተርታ መቀላቀላቸውን የገለጸው የአለም ባንክ፤ አርጀንቲና፣ ሃንጋሪ፣ ሲሸልስና ቬንዙዌላ በበኩላቸው ደረጃቸውን በማሻሻል አምና ከነበሩበት ከፍተኛ መካከለኛ ገቢ ወደ ከፍተኛ ገቢ አገራት ሸጋግረዋል ብሏል፡፡በአመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ ከአለማችን አገራት ዝቅተኛውን ደረጃ የያዘችው ማላዊ ናት ያለው የአለም ባንክ፤ በ2014 የነፍስ ወከፍ ገቢዋ 250 ዶላር ብቻ የሆነው ማላዊ፣ ባለፉት 24 አመታት
የነፍስ ወከፍ ገቢዋ የጨመረው በ70 ዶላር ብቻ ነው ብሏል፡፡ በአንጻሩ በአመቱ ከፍተኛውን የአለማችን አመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ ያገኘችው የፈረንሳዩዋ ከተማ ሞናኮ ስትሆን፣ የነፍስ ወከፍ ገቢው ከ100 ሺህ ዶላር በላይ ነው ተብሏል፡፡በአለም ባንክ መስፈርት መሰረት፤ አመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢያቸው ከ12ሺህ ዶላር በላይ የሆኑ፣ ከፍተኛ ገቢ፤ ከ12 ሺ 735 እስከ 4ሺህ 126 ዶላር የሆኑ፣ ከፍተኛ መካከለኛ ገቢ፣ ከ4ሺህ 125
እስከ 1ሺህ 46 ዶላር የሆኑ፣ ዝቅተኛ መካከለኛ ገቢ፤ ከ1ሺህ 45 ዶላር በታች የሆኑ፣ ዝቅተኛ ገቢ
ያላቸው አገራት ተብለው ይመደባሉ፡፡

Published in ዜና