በደራሲ ገነት አዲሱ የተፃፈው “የማንነት አደራ” የተሰኘ የረዥም ልብወለድ መጽሐፍ ባለፈው እሁድ በራስ አምባ ሆቴል የተመረቀ ሲሆን ከሳምንቱ መጀመሪያ አንስቶ በመሸጥ ላይ እንደሆነ ታውቋል፡፡
“ከዓመታት ጀምሮ በርካታ ሃሳቦች በውስጤ ከወዲያ ወዲህ ሲሉ ኖረዋል፤ እነሆ ዘመናቸው መጥቶ በአምላክ እርዳታ ቃሎች ከጥበብ ጋር እንደመዋደድ ያሉልኝ ሲመስለኝ ዛሬ ሃሳቦቼ ጽሑፍ ሆነው ሊወለዱ ደፈሩ” ብላለች፤ ደራሲዋ በመፅሀፉ መግቢያ ላይ ባሳፈረችው ሃሳብ፡፡
በ376 ገፆች የተቀነበበው መጽሐፉ፤ ለአገር ውስጥ በ94 ብር፣ ለውጭ በ25 ዶላር ለገበያ ቀርቧል፡፡ ደራሲዋ በኢንተርናሽናል ቴኳንዶ በአፍሪካ የመጀመሪያውን 4ኛ ዲግሪ ያገኘች የማርሻል አርት አስተማሪ ስትሆን “አላዳንኩሽም” እና “ምርቅዝ በቀል” የተሰኙ ፊልሞች ላይ በመተወንም ትታወቃለች፡፡

    በህፃናት ላይ የሚሰራው ዊዝ ኪድስ፣ በ7 ሃገርኛ ቋንቋዎች የተለያዩ የህፃናት መፅሃፍትን ለማዘጋጀት ማቀዱን ገለጸ፡፡ መፅሃፎቹ በአማርኛ፣ በትግርኛ፣ በሃዲያ፣ በሶማሊኛ፣ በሲዳሞኛ፣ በኦሮምኛና በወላይትኛ ቋንቋዎች የሚዘጋጁ ሲሆን በቀጣይ ሳምንት በሚያካሂደው የ7 ቀናት ወርክሾፕ ላይ የመፅሃፎቹ ዝግጅት ይከናወናል ተብሏል፡፡
ከመስከረም ወር ጀምሮም መፅሃፎቹ ለገበያ እንደሚቀርቡ ተጠቁሟል።  የዊዝ ኪድስ ወርክሾፕ ዋና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ብሩክታዊት ጥጋቡ፤ ድርጅታቸው በአዲሱ ትውልድ ልብ ውስጥ የንባብ ልማድና ፍቅርን ለማስረጽ በማለም ወደ መፅሃፍት ዝግጅት መግባቱን ጠቁመው፣ የህፃናትና  ታዳጊዎች ንባብ መጎልበት ሃገሪቱ ለምትሻው የትምህርት ጥራት አጋዥ ይሆናል ብለዋል፡
በሰባቱ ሃገርኛ ቋንቋዎች የሚዘጋጁት መፅሃፍቱ፤ህፃናትን የሚያነቃቁ የተለያዩ ታሪኮችና ርዕሰ ጉዳዮችን የሚያካትቱ  ይሆናሉ፤ የህፃናቱን እድሜ የሚመጥኑ እንዲሆኑም ይደረጋል ተብሏል፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር የዘርፉ ተግዳሮቶች ብሎ ከጠቀሳቸው መካከል አስፈላጊ የሆኑ አጋዥ መፅሃፍት እንደልብ አለመገኘት አንዱ መሆኑን የጠቀሱት ወ/ሮ ብሩክታይት፤ ድርጅታቸው ይህን እጥረት ለመቅረፍ ከትምህርት ስርአቱ ጋር የተጣጣሙ ጥራት ያላቸውን ተነባቢ መፅሀፍት በተለያዩ የሃገሪቱ ቋንቋዎች ማዘጋጀቱን ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ዊዝ ኪድስ በአሁን ወቅት እድሜያቸው ከ3-17 ዓመት ለሆናቸው ህፃናትና ታዳጊዎች 3 የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን እያዘጋጀ ሲሆን ከዚህ ቀደም በ5 ሃገርኛ ቋንቋዎች፣ከ35 በላይ የህፃናት መፅሃፍት አሳትሟል፡፡

የታዋቂው ፖለቲከኛ ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም“አዳፍኔ” ፍርሃትና መክሸፍ” የተሰኘ “መጽሐፍ
ባሳለፍነው ሣምንት ለንባብ በቅቷል፡፡ደራሲው ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም “ሐውልት”በሚል ርዕስ ባሠፈሩት የመታሰቢያ ገፅ ጽሑፋቸው፤ለደጃዝማች ሃይሉ ከበደ፣ ዋጋቸውን ላላገኙለኢትዮጵያ አርበኞች፣ የፋሽስት ኢጣሊያን ወረራለመቋቋም በእንግሊዝ አገርና በአውሮፓ በሙሉየተደረገውን የፖለቲካ ትግል የነጭ ዘረኛነትን አጥሮችሁሉ ተሻግረው ሰው በመሆን በፊታውራሪነትለመሩት ይዘሮ ሲሊቪያ ፓንክረስት፣ የዜግነትግዴታቸውን በአውሮፓ በተለያዩ መንገዶች ለፈፀሙለፀሐፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሃብተወልድ፣ ለአብዲሣ አጋእና ለዘርአይ ደረስ ይሁን ብለዋል፡፡መጽሐፉ የተለያዩ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እናታሪካዊ ጉዳዮችን የሚተነትን ሲሆን በ280 ገፆችተዘጋጅቶ በ69 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡

በአብነት ስሜ የተጻፉት “የቋንቋ መሰረታዊያን” እና “ሳይኪና ኪዩፒድ” የተሰኙ ሁለት መጽሃፍት ካለፈው ረቡዕ ጀምሮ ለገበያ መብቃታቸውን ጸሃፊው በተለይ ለአዲስ አድማስ ገለጸ፡፡
በቋንቋ ምንነት፣ አመጣጥ፣ የመማር ሂደት፣ ተግባራትና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥነውና 407 ገጾች ያሉት መጽሃፉ፤ በ90 ብር ከ99 ሣ. በአዲስ አበባ እና በተለያዩ ክልሎች በመሸጥ ላይ ይገኛል፡፡ በስድስት ክፍሎችና በአስራ አራት ምዕራፎች የተከፋፈለው መጽሃፉ፣በቋንቋ እና እሳቦት፣ በቋንቋ ሳይንሳዊ ጥናት እንዲሁም በጽህፈት ታሪክ ዙሪያ በጥናት የተደገፉ መረጃዎችንና ትንተናዎችን አካትቷል ተብሏል፡፡
ለገበያ የቀረበው ሌላኛው የደራሲው ስራ “ሳይኪና ኪዩፒድ” የተሰኘ የህጻናት መጽሃፍ ሲሆን አስር ተረቶች፣ አራት መቶ እንቆቅልሾችና አንድ የእንግሊዝኛ ልቦለድ አካትቶ የያዘ ነው፡፡   
አብነት ስሜ ከዚህ ቀደምም “የኢትዮጵያ ኮከብ” እና “ፍካሬ ኢትዮጵያ” የተሰኙና በኮከብ ትንበያ፣ ትንተና እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ መጽሃፍትን ለንባብ ማብቃቱ ይታወሳል፡፡





በማህበራዊና ትምህርታዊ ጉዳዮች ላይ በማተኮር የምትዘጋጀው “ተምሳሌት” መጽሔትና ዌብሳይት የምረቃ ሥነስርዓት ዛሬ ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ በዋቢሸበሌ ሆቴል ሆቴል ይካሄዳል። መጽሔቷ ባለሙሉ ቀለም ህትመት መሆኗን የገለፁት አዘጋጆቹ፤ በአዲስ አበባና በዙሪያው ባሉት ከተሞች እንደምትሰራጭም ገልፀዋል፡፡ ተምሳሌት ዌብሳይት ከመጽሔቷ ጋር በተጓዳኝ አገልግሎት እንደሚሰጥም ታውቋል፡፡
በምረቃ ሥነስርዓቱ ላይ “ተምሳሌት” መጽሔት እና ዌብሳይትን የማስተዋወቅ ፕሮግራም እንዲሁም የፓናል ውይይት ይካሄዳል ተብሏል፡፡


“እኔን ፅሁፍ ለማስጣል ይህ ሁሉ ጣጣ አያስፈልግም፡፡ ብትጠይቂኝ ዘዴውን እኔው እነግርሽ ነበር፡፡ ዘዴው ምን መሰለሽ? ቀላል ነው። ላንድ ወር በየቀኑ ዶሮ ማረድ፡፡ ያንን በእርጐ እያደረግሽ ማቅረብ፡፡ ክትፎም ቢጨመርበት ይበልጥ ፍቱን ይሆናል፡፡ በዚያ ላይ ቀዝቃዛ ቢራ በቃ፡፡ የጽሑፍ ነገር እርግፍ ብሎ ይቀራል፡፡  አረቦች እንደሚተርቱት፤ ‹ሆድ ሲሞላ ጭንቅላት ባዶ ይሆናል› ከዚህ የበለጠ ምን ዘዴ አለ?...”
(በዓሉ ግርማ “ደራሲው”)
በዓሉ ግርማ ደራሲን የደራሲነት “ትጥቅ” የሚያስፈታው ጥጋብ እንደሆነ እየነገረን ነው፡፡ ጥጋብ የሰው ልጆች ሁሉ የምንማስንለት ተፈጥሯዊ ግብ አይደለምን? ታዲያ ደራሲን ከሰው ልጆች ተርታ ምን አስፈንጥሮ ወረወረውና ረሃብ ሠራሽ ሆነ? ደራሲነትን ከግርንቢጥነት ያጋባ ገለፃ ነው፡፡ ለመሆኑ ደራሲ ምንድነው? ሰው ሁሉ በሚደርቅበት ቦና የሚለመልም? በሚያሸትበት የሚረግፍ ግርንቢጥ? እንዴት በሚበርደው ይሞቃል? በሚያቃጥለው ይንዘፈዘፋል? ደራሲን በደራሲነት የሚያተጋው ረሃብ ነው ማለት ነው? እንዲያ ከሆነ አንድ ነባር ብሒል እንዋስ፡-
“ከተራበ ደራሲ ለጠገበ ደራሲ አዝናለሁ!”
ይሄንኑ የበዓሉ ግርማን አባባል ከሌላ አቅጣጫ አይቶ የደገመ የሥነ - ልቡና ምሁር አለ፡፡ ስኮትላንዳዊው የፍካሬ - ልቡና (Psychoanalysis) መስራች ሲግመን ፍሩድ ነው፡፡ ጥበብን ከሆድ ሳይሆን ከወሲብ አቅጣጫ ያየዋል፡፡ አንድ የጥበብ ሰው የታመቀ የወሲብ ፍላጐት (Libido ወይም repressed sexual desire) ከሌለው ባሩድ እንዳነሰው ጥይት ቢተኮስም ይከሸፋል ባይ ነው። ጥበብ በወሲብ ረሃብ እንጂ በፍትወት ጥጋብ አትገኝም፡፡ የታመቀ የወሲብ ፍላጐትን ለጥበብ አላማ በማዞር (Sublimation) ግሩም ውጤት ማግኘት ይቻላል ብሎ ያምናል፡፡
የበአሉንም ሆነ የሲግመን ፍሩድን ብያኔ የሚፃረሩ ደራሲያን ዘንድ ተከስተዋል፡፡ ከሁለቱም አንድ አንድ ደራሲ ከ “ጣዝማ” መጽሐፍ እንጥቀስ፡፡ ፈረንሳዊ የልቦለድ ደራሲ ኖርማንድ ግራ የሚያጋባና የሚደንቅ የአመጋገብ ልምድ እንደነበረው እዚህ መጽሐፍ ላይ ይጠቀሳል፡፡ “መቶ የሼል አሣዎች ከቀማመሰ በኋላ ከጠቦት በግ አሥራ ሁለት ሙዳ ሥጋ ያክልበታል፡፡ በዚህ አያበቃም፡፡ ከጥሩ አትክልት ጋር የተዘጋጀች አንድ ዳክዬና የሁለት ቆቆች አሮስቶ ጨምሮ ሲጥ ያደርጋል፡፡ ከዚህ በኋላም የበላውን ምግብ ለማወራረድና በጐደለ ለመሙላት የተለያዩ ፍራፍሬዎችን እንዳመሉ ልክክ አድርጐ ቡናና ልዩ ልዩ መጠጦችን ደህና አርጐ በጉሮሮው ያወራርዳል።”
ከፆታ ግንኙነት አንፃር የተለዩ ደራሲዎች በሚወሱበት ንዑስ ርዕስ ሥር ደግሞ አሌክሳንደር ዱማስ ፔሪ ተጠቅሷል፡፡ ዱማስ ፔሪ የአምስት መቶ ዲቃላ ልጆች አባት ነበር፡፡ በቁጥር ልድገመው ይሆን? የ500 ልጆች አባት፡፡
ደራሲና ድርሰት “ሰው ሲሏቸው አፈር፣ አፈር ሲሏቸው ሰው” ናቸውና በተወሰነ ቅንብብ ውስጥ ከትሮ ማስቀመጥ ይከብዳል፡፡ የበዓሉን አቋም ሆነ የፍሩድን ሥነ - ልቦናዊ ግኝት በትክክልነት በህይወታቸው የተረጐሙ ደራሲዎች አይጠፉም፡፡ ከዚህ አንፃር እኔ የማውቀው እንግሊዛዊው ደራሲ ዲ ኤች ላውረንስ ነው፡፡ ላውረንስ የፍሩድን ፅንሰ ሀሳብ ሙሉ በሙሉ ከመቀበሉ የተነሳ “Psychoanalysis” የሚል አንድ የጥናት መፅሐፍ ጽፏል፡፡ ላውረንስ ከመጽሐፉ ያተረፈው ሽሙጥ ብቻ ሆነ እንጂ ሐያሲያን “ሲግመን ፍሩድን ከእንግሊዝኛ ወደ እንግሊዝኛ የተረጐመ” አሉት፡፡
ላውረስ እንደ በዓሉ ሁሉ “ሆድ ሲሞላ ጭንቅላት ባዶ ይሆናል” ያለ ደራሲ ይመስላል፡፡ በሥራው ብቻ ሳይሆን በህይወቱም እንደዚያ ነበር፡፡ እንክብካቤ ያስመመረው፣ ድሎት የጐፈነነው፡፡ ደራሲነቱ በእንክብካቤና በድሎት እየተዳፈነ እንደሆነ የተሰማው ላውረንስ፤ ለቤተሰቡ አራተኛ ልጅ ነው፡፡ የእሱ ታላቅ ወንድም ለእናታቸው ተወዳጅ ልጅ ነበር፡፡ እንክብካቤዋን በፍቅር የሚቀበል። ነገር ግን ባልታሰበ ሁኔታ ድንገት ታሞ፣ ድንገት ሞተ፡፡ ላውረንስ ወንድሙ ላይ አርፎ የነበረው ያ ሁሉ ፍቅርና እንክብካቤ ሲያርፍበት የደራሲነት      “ወገቡ” ተልመጠመጠ፡፡
“በላህ?”
“አዎ”
“ጠጣህ?”
“አዎ”
“እችን ድገምበት”
“በልቼ? ጠጥቼ?”
“እሺ እንዳይበርድህ ደርብ”
ላውረንስ እናቱን ሊዲያ ላውረንስን ጠላት፡፡ እንደውም አንዳንድ መጽሐፍ ላይ እንድትሞትለትና ነፃ እንዲወጣ ተመኘ ይሉታል፡፡ የተመኘው ተሳክቶለት እናቱ ስትሞት አንድም ሀዘን ልቡናውን አልዳሰሰውም፡፡
እስር ቤቱ እንደተሰበረ ቆጠረው እንጂ፡፡ እንዲህ የሚገምቱ ሰዎች ከላውረንስ ልቡና ጋር በተአምር ተማክረው አልነበረም፡፡ ከዚያ በኋላ በፃፈው “Sons and Lovers” ልቦለድ ውስጥ ህይወቱን ስለተረከው እንጂ፡፡
እዚህ ልቦለድ ውስጥ እናቱና ፍቅረኛው የድሎት እስር ቤት የሚሆኑበት ዋና ገፀ - ባህርይ አለ፡፡ በተለይ እናቱ እንድትሞትለት ይመኛል፤ ስትሞት ከማዘን ይልቅ ፈገግ ይላል፡፡ “ያ ገፀባህርይ ላውረንስ ነው” የሚሉ ሃያሲያን አሉ፡፡ የፃፈው ህይወቱን፣ ኑሮውን፣ ምኞቱን ነው…
…ይሆን እንዴ? እንዲያ’ኮ ከሆነ የደራሲ ግርንቢጥነት ተባባሰም አይደል? ተድላው ችግር፤ ችግሩ ተድላው መሆኑም አይደል?

Published in ጥበብ

በፌስቡክ  ለአመታት የተለያዩ ጽሁፎችን በማቅረብ የሚታወቁ ጸሃፊያን በጋራና በተናጠል ያሳተሟቸውን የግጥም፣ የአጫጭር ልቦለዶችና የወጎች ስብስብ መጽሐፍትን ለንባብ እያበቁ ነው፡፡
የአምስት ገጣሚያንን ስራዎች ያሰባሰበው “መስቀል አደባባይ” የተሰኘ የግጥም መድበል ባለፈው ማክሰኞ ገበያ ላይ የዋለ  ሲሆን፣ በፌስቡክ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ሂሶችንና ወጎችን በማቅረብ ተወዳጅነትን ያተረፈችው  ህይወት እምሻውም “ባርቾ”በሚል ርዕስ  የአጫጭር ልቦለዶችና የወጎች ስብስብ መጽሃፍ አሳትማለች፡፡
በግጥም መድበሉ የአሌክስ አብርሃም፣ ዩሃንስ ሃብተ ማርያም፣ ረድኤት ተረፈ፣ ዮናስ አንገሶም ኪዳኔ እና ፈቃዱ ጌታቸው ግጥሞች የተካተቱ ሲሆን፣ ገጣሚያኑ እያንዳንዳቸው አስር ግጥሞችን አቅርበዋል፡፡ 150  ገጾች ያሉት የግጥም መድበሉ፣ በ45 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡
የግጥም ስራዎቹን በማሰባሰብ ለህትመት ያበቃው ገጣሚና ደራሲ አሌክስ አብርሃም በተለይ ለአዲስ አድማስ እንደገለጸው፣ መስቀል አደባባይ በቀጣይም በቅጽ ተከፋፍሎ ለህትመት የሚበቃ ሲሆን፣ በፌስቡክም ሆነ በተለያዩ መድረኮች የሚታወቁ ወጣትና አንጋፋ ጸሃፊያንን የግጥም፣ የወግና የልቦለድ ስራዎችን የሚያካትት ይሆናል፡፡ የመስቀል አደባባይ ሁለተኛ ቅጽ ዝግጅት በከፊል መጠናቀቁንም አሌክስ አብርሃም ጠቁሟል፡፡
በሌላ በኩል ወጎችን፣ አጫጭር ልቦለዶችንና በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ መጣጥፎችን  በፌስቡክ በስፋት በማቅረብ የምትታወቀውና በርካታ ተከታዮችን ያፈራችው ህይወት እምሻው፣ የመጀመሪያ ስራዋ የሆነውን ባርቾ የተሰኘ የወጎችና የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ መጽሃፍ፣ ለህትመት አብቅታለች፡፡ 31 ወጎችን፣ 8 ልቦለዶችንና 13 የመሸጋገሪያ አጫጭር ልቦለዶችን ያካተተውና 256 ገጾች ያሉት መጽሃፉ፣ የመሸጫ ዋጋው 60 ብር እንደሆነ ደራሲዋ ለአዲስ አድማስ የገለጸች ሲሆን የፊታችን ሐሙስ  በዋቢ ሸበሌ ሆቴል እንደሚመረቅ ተናግራለች፡፡
በዕለቱ ከ11፤30 ሰኣት ጀምሮ በሚካሄደው የምረቃ ስነስርዓት ላይ በመጽሃፉ ከተካተቱት ታሪኮች አንዱ በአጭር ድራማ መልክ ለታዳሚዎች የሚቀርብ ሲሆን፣ የሙዚቃና የግጥም ስራዎችም ይቀርባሉ፡፡
ፌስቡክ ለበርካታ ወጣትና አንጋፋ ጸሃፍያን ስራዎቻቸውን ለአንባቢ ለማድረስ ሁነኛ አማራጭ እየሆነ የመጣ ሲሆን በማህበራዊ ድረገጹ ላይ በመጻፍ የሚታወቁ በርካቶችም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስራዎቻቸውን በመጽሃፍ መልክ እያሳተሙ በስፋት ለንባብ ማብቃት ጀምረዋል፡፡
በፌስቡክ ከሚታወቁና ከዚህ ቀደም ስራዎቻቸውን ለህትመት ካበቁ ጸሃፊያን መካከል፣ አሌክስ አብርሃም፣ በረከት በላይነህ፣ ሮማን ተወልደ ብርሃን፣ ዮሃንስ ሞላ፣ ሃብታሙ ስዩም፣ ቢኒያም ሃብታሙ፣ ትዕግስት አለምነህ፣ ሄለን ካሳ፣ ዮናስ አንገሶም ኪዳኔ፣ ሜሮን አባተ፣ ብሩክታዊት ጎሳዬ፣ ስመኝ ታደሰ እና ሌሎችም ይገኙባቸዋል፡፡

Saturday, 04 July 2015 10:51

እንደ እያሪኮ

ድንገት ድምፁን በሙሉ ማን አጠፋው? ዛሬ ምን ተገኘና ከተማው አንድ ላይ እረጭ አለ? ትላንት ልጽፍ ነው ብዬ ስቀመጥ…አለሙ አንድ ላይ ተነስቶ ሲጮህብኝ አልነበር? እነዛ ዘመናቸው ሳይደርስ በእኔ ትውልድ ላይ ተለጥፈው የተወለዱ ህፃናት እሪ እያሉ ቤቴን ሲዞሩት… ጐረቤቴ ያለው ሰው በፆም ሆዱ በፍስክ ምኞቱ እየጮኸ ሲያደነቁረኝ አልነበረም…ዛሬ ታዲያ ሁለተኛ አልፅፍም ብዬ ምዬ፣ ብዕሬን በድራፍት ውጬ  ከሰፈሬ በጣም ርቄ በተቀመጥኩበት--- ጭጭታው ከየት መጣ?
ድምፁ እንደተቀነሰ ቴሌቪዥን ከተማው ያለ ድምጽ ከፊቴ ይንቀሳቀሳል፡፡ ችኩልነቱን በስክነት የቀየረው በደንብ እንዳስተውለውና እንድፅፈው ነው አይደል? የፈለገ ብታምርም አልጽፍህም፡፡ ትላንት ሳባብልህ አሻፈረኝ ብለኸኛል፡፡ ሳሰላስል አናቴ ላይ ባዶ ሙቀጫ አስቀምጠህ ወቅጠህብኛል፡፡ ስለዚህ ዛሬ ቢያምርብህም፣ ሰክነህ መፃፍ ብትሻም እኔ አልተባበርህም፡፡
አድባሪቷ ዛሬ መጥታለች፡፡ እና ምን ላድርግልሽ? ትላንት ስጠብቅሽ፣ ብዕሬን በሰም ወልውዬ ልቦናዬን ለሩቅ ምናኔ መትሬ፣ ጥሞናን ስሻ ጠፍተሽ፣ ዛሬ ለጩኸት የክት ረብሸኛነቴን ለብሼ ብወጣ ጭጭ ብለሽ መጣሽብኝ። ዛሬ ለጠብ ዝግጁ ነኝ፡፡ ለመናደድ ነው ቀጠሮ የያዝኩት፡፡ የትላንቱ ቀን እስቲ ወንድ ዛሬ ይምጣ!...
እየው…እዛ ማዶ አንዱ መዶሻ ይቃጣና የተቃጣበትን ሚስማር ይዶሸዋል፡፡ ግን ድምጽ እንዲያወጣ በሃይል ይቃጣና ሚስማሩ አናት ጋር ሲቀርብ ቀስ ብሎ ያሳርፋል። ደግሞ ቀና ይልና እኔን ያየኛል፡፡ በአይኑ ያባብለኛል። የፈለገ ብትለሳለስ አልጽፍህም! አለቀ… ይልቅስ አንተኛው ድራፍት ድገመኝ፡፡ አዎ አስተናጋጁ እንዲሰማ ጠረጴዛውን በደንብ አድርጌ እነርተዋለሁ፡፡ የብርጭቆው እጀታ እስኪረግፍ፡፡
ለምንድነው ይኼ ጠረጴዛ እንደ እስፖንጅ ስደልቀው ትሙክ የሚለው፡፡ አራት ድራፍት ነው የጠጣኸው ሲለኝ (በጆሮዬ ተጠግቶ በሹክሹክታ)…እኔ እየጮሁኩ ሁለት ነው ብዬ ክርክር መፍጠር ፈልጌአለሁ፡፡ አበሳ የሚያመጣ ክርክር፡፡ ብርጭቆ አወራውሮ የሚያፈናክት አይነት ክርክር፡፡
ለምንድነው የጠጣሁትን ቀንሼ ስከራከረው “ይሁንልህ” ብሎ ሸብረክ ከማለት ባላነሰ ተስማምቶ የሚሄደው፡፡ ቀስ ብዬ ብርጭቆውን ገፍቼ መሬቱ ላይ ብጥለው ፀጥታው ይበጠበጣል፡፡ ፀጥታውን ለማጥፋት ስል የብርጭቆውን ዋጋ ተደብድቤ ብከፍል ይቀለኛል፡፡ እልህ ይዞኛል፤ ትላንት እንደ በጠበጡኝ… ዛሬ በተራቸው ጩኸትን መቅመስ አለባቸው፡፡
አድባሪቷ መጥታ ከእኔ ጋር ተቀምጣለች። እንደማላውቃት ያላየሁዋት ብመስልም አይቻታለሁ። ውበቷን አሰማምራ፣ መቶ አምፖሏን አብርታ ነው የመጣችው፡፡ መጽሐፍ፣ ወረቀት እና ውድ እስኪርብቶ ገዝታልኝ መጥታለች። እየተቁለጨለጨች አይን አይኔን ታየኛለች፡፡ የለበሰችው ጉርድ ቀሚስ ባቷን ያሳያል፡፡ በጣም ለመፃፍ የሚያጓጓ ባት ነው፡፡ እየፃፍኩ ብገልበው ውስጥ ሱሪዋን አገኘዋለሁ፡፡ እየፃፍኩ ባወልቀው በጣም የሚያረካ ድርሰት ሆና ነው የመጣችው፡፡ ግን የፈለገ ቢዮንሴን ብትመስል ዛሬ አልጽፋትም። ሌላ ፀሐፊ ጋ ትሂድ፡፡ ግን አሳምሬ አውቃለሁ፤ የኔይቱ አድባር ሌላ ማንም ጋ መሄድ እንደማትችል። ወይንስ ትችላለች?! ትላንት የት ነበር የሄደችው? ማንን ተኝታ ነው የመጣችው፡፡
ድንገት ቅናት በልቤ ውስጥ ተደመረ፡፡ የመስቀል ደመራ፡፡ ግን ደመራው ፀጥ ያለ ነው። እሳት ይንቀለቀላል እንጂ ድምጽ አያወጣም!...ለዚህች ቀልቃላ አድባር… በቅናት ነዶ መንቀልቀል አያስፈልግም፡፡ “ለምን እንደሄድሽ አልቀረሽም? የሄድሽው ደራሲ እንደምትፈልጊው አላደረገሽም? ነካክቶ ተወሽ?” አልኳት፡፡ ግን ምላሴ ላይ ዘይት ማን እንደቀባኝ አላውቅም፤ ቃላቶቼ እያሟለጩ ትርጉም ሳይሰጡ ተዝረክርከው ቀሩ፡፡
“እ” አለችኝ እግሯን ፈትታ እያጣመረች፡፡ ፈትታ ስታስረው በብልጭታ የውስጥ ሱሪዋ ቀለም ይታየኛል። በጥቁር ከሰል ላይ በደንብ የተርገበገበ ቀይ ፍም ያየሁ መሰለኝ፡፡ ሰክሬአለሁ መሰለኝ፤ የአንደበቴ መቋጠሪያው ላልቷል፡፡ የፊኛዬ መቋጠሪያ ግን በደንብ ይሰራል፡፡ ፊኛዬ ተወጥሯል፡፡ ግን ዛሬ አልጽፍም ብያለሁ፡፡ መቋጠሪያዬ ይሰራል፡፡ ዛሬም ነገም አልጽፍም፡፡ እሷም ሌላ ዘንድ ትሂድ…
እኔም ራሴን መግዛት በቅጡ ልልመድበት። እንደው በጥበብ ፍቅር ስም በሷ ገላ ላይ ሰርክ የማልሰለች ኮርማ ሆኜ አርፌአለሁ፡፡ ከተማው እኔ ለእሷ ላለኝ ፍቅር ብሎ ፀጥ ቢልም እኔ ግን እሷን አልጽፍም፡፡ ወረቀት ላይ እሷን በመተኛት እድሜዬን አባከንኩ፡፡ እሷም ወይ ልጅ አልወለደች እንዲሁ ወረቀት እና ቀለም ማልፋት ብቻ፡፡
መጋባት እና ልጅ መውለድ ወይንም መለያየት። ይሄው ነው መፍትሔው፡፡ አንድ ቀን ጩኸት ሌላ ቀን ፀጥታ እያፈራረቁ ግራ መጋባት ከእንግዲህ አይሰራም። በአፌ ከምናገረው ይበልጥ የማስበውን ማድመጥ ትችላለች አድባርዬ አድባሪቱ፡፡ እግሯን መከፋፈት ትታ ቀሚሷን ወደ ታች እየሳበች ረዥም ቀሚስ አደረገችው፡፡ ኩርምት ብላ ማሰብ ያዘች፡፡
“እኔን ካገባህ እድሜ ልክ ፀጥታ እና ጥሞናን ታገኛለህ፡፡ ግን እድሜ ልክህን ደሀ ነው የምትሆነው…ይሄንን አውቀህ ከተቀበልክ መጋባት እንችላለን” አለችኝ፡፡
በፊት በጣም እርግጠኛ ነበርኩ - እቺን ሴት ማግባት ስለመፈለጌ፡፡ አሁን ግን ድንገት ጥርጣሬ ገባኝ፡፡ ልጅ መውለድ እፈልጋለሁ፤ ግን ከማታስተማምን አድባር ጋር ተጋብቼ፣ በአንድ ሴት መወሰን መቻሌን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡
“ላስብበት” አልኳት፡፡
ቀጠሮ ሰጥታኝ መጽሐፍቷን እና መፃፊያ ቁሳቁሷን ይዛ ወጣች፡፡ ስትወጣ ቅር አለኝ፡፡ ቀደም ብዬ በእልህ የዋጥኩት እስክሪብቶም ደረቴን እየፋቀ ቃር ለቀቀብኝ። እሷ ስትወጣ ድንገት ከተማው ዛሬ መሆኑ ቀርቶ ትላንት ሆነ፡፡ ፀጥታው በጫጫታ ተተካ፡፡ እንደ እያሪኮ በጩኸት ፈረሰ፡፡ የብርጭቆዎቹ ኳኳታ ጆሮዬን ሰብረው ገቡ። ብርጭቆዎች መዶሻ ሆኑ፡፡ ወሬዎች እንደሚስማር የሰውን ብቸኝነት ከቡድን ወሬዎች ጋር ወስደው መስፋት ጀመሩ፡፡ ድምፆች ሲጐሉ የእኔ ድምጽ ደግሞ ውጪውን ፈርቶ አልወጣም አለ፡፡ ብርጭቆውን በቀስታ ማንሳት ጀመርኩ፡፡ የራሴ ልብ ምት መሸሸጊያ አሳጣኝ፡፡ ከሰፈሬ በጣም ብርቅም ጐረቤቶቼ የሚወቅጡት ሙቀጫ ጐልቶ የተቀመጥኩበት ቦታ ድረስ እየጮኸ መጣ፡፡
አድባሪቱ ከመሄዷ በፊት ላስቆማት ወጣሁኝ። ጠረኗን ተከትዬ፣ የዱካዋን ፊደሎች አሽትቼ፣ ቆማ ገላዋን ለአላፊ አግዳሚ ወደምታስጐበኝበት የመንገድ መብራት ስደርስ ዋጋ እየተደራደረች አገኘሁዋት፡፡ ሌላ ፀጥታን ፈላጊ አባብሎ ሊወስዳት ነው፡፡ ገና አጠገቧ ከመድረሴ…አካባቢውን በውበት ሞልታዋለች፡፡ የመንገዱን መብራት ጨረቃ አድርጋዋለች፡፡ አስፋልቱ አረንጓዴ መስክ መስሏል። የማስታወቂያ ሰሌዳ ቋሚዎቹ እንደ ሰንበሌጥ ይወዛወዛሉ፡፡
ልታስተምረኝ የፈለገችው ነገር ገባኝ፡፡ ያለ እሷ መኖር አልችልም፡፡ ከሁለታችን ኩርፊያ ጉዳቱ የሚያደላው በእኔ ላይ ነው፡፡ ሊቀድመኝ ከሚያባብልብኝ ሰው እጅ አስጥዬ አቀፍኳት፡፡ ብዙም አልተግደረደረችም፡፡ ተሳመችልኝ። ተመልሶ ፀጥታ በአለም ላይ ሰፈነ፡፡ ወደ ቤቴ…እና ቤታችን ከንፋስ በቸኮለ አከናነፍ ደረስን፡፡
አልጋውን ጠረጴዛ አድርጌ አዘጋጀሁት፡፡ አንሶላውን በወረቀት ለወጥኩኝ፡፡ እንደማትጠገብ አድርጌ.. ቶሎ እንዳታልቅ… ሌሊቱን አክላ እንድትቆይ አድርጌ ቀስ በቀስ እየገለጽኩ እስኪነጋ ስፅፋት አደርኩኝ፡፡


Published in ጥበብ

    መረን የወጣ የፍትወት ልማድና አፈንጋጭ ወሲባዊ ልምምድ እጅግ የቆየ የማህበረሰብ ልማድ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሶዶማውያን የቀለጡበት፣ ጥንታውያኑ ግሪኮች የኖሩበት፣ ለሮማውያኑም ውድቀት እንደ ምክንያት ተደርጎ የሚዘከርለት ነው። የፍቅር ግንኙነት አካል ከሆኑ ጉዳዮች መካከል በበጎም ሆነ በመጥፎ ጎኑ እንደ ፍትወት/ወሲብ የተነገረለት የለም። ይህንኑ በሚመስል ርዕሰ ጉዳይ ላይ አንድ የአገራችን ምሁር “አውሬ ያለ ጫካ አይኖርም!” እንዳሉትም ከገንዘብና ከሥልጣን ጥማት በትይዩ የብዙ አውሬነቶች መፈልፈያው ጫካ በሰው ልጅ የፍትወት ፍላጎት ውስጥ ይገኛል፡፡ በእርግጥ በማህበረሰባችን ዘንድ ስለ ወሲብ መነጋገር ማለት በአመዛኙ ስለ “ባለጌ ነገር” እንደማውራት ይቆጠራል፡፡ ሆኖም ገና ከአፍላነት እድሜ አንስቶ ወሲብን በቀልድና በጫወታ መካከል ጣል የሚያደርግ ሰው ሲገኝ ጆሮ መስጠትና ነቅቶ ማድመጥ የተለመደ ነው፡፡
   የጋብቻና የሥነ ወሲብ አማካሪው ቲም ላሃዬ፤ “በጊዜያችን ወሲብ ከፍቅር ሙሉ በሙሉ ተነጥሏል፣ ከፍ ተደርጓልም፣ ወሲብ ከፍቅር በፊት መምጣቱ የተለመደ ሆኗል” ይላሉ፡፡ “አንድ ግንኙነት የሚጀምረው ወይም የሚቋጨው በወሲብ ነው” የሚሉት ቲም ላሃዬ፤ “ወሲብ ልክ እንደ ቴኒስ ጨዋታ ከአንድ ከሚያውቁት ሰው ጋር የሚፈፀም ሆኗል፤ከፍቅር ይልቅ አፅንኦት የሚሰጠው ለወሲብ ነው፡፡ እንዴት ‹ጥሩ› ሆኖ እንደተፈጸመና አስደሳችነቱ የሚለካው በእርካታው መጠን ነው” የሚሉት ላሃዬ፤ ወሲብ የፍቅር ግንኙነት አካል እንጂ ብቻውን ተነጥሎ የሚመነዘር ርካሽ ነገር ያለመሆኑን ይገልጻሉ፡፡ “ወሲብ መልካምና አስደሳች የሚሆነው ግልፅነት፣ መተማመን፣ ጓደኝነትና ፍቅር ሲኖር ብቻ ነው፤አርኪ ወሲብ ምን አይነት እንደሆነ የሚያውቁ ሰዎች የብልቶች መገናኘትና ከእርካታ ጫፍ መድረስ ብቻቸውን በቂ እንዳልሆኑ ይገነዘባሉ” ይላሉ፡፡
በሰለጠኑት አገሮች ጤናማው የወሲብ መረዳት ምን መምሰል እንዳለበት የሚመክሩ ብዙ መፅሐፍት  ተፅፈዋል፡፡ በዚህች በእኛዋም አገር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተሞከሩ ያሉና ይበል የሚያሰኙ ሥራዎች ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል፡፡ ዕድሉን አግኝቼ  በተካፈልኩባቸው አንድ፣ሦስት ያህል አውደ ጥናቶች ላይ ስለ ጉዳዩ የተደረጉ ውይይቶችን ባደመጥኩበት ጊዜም ‹‹ለካስ ወሲብ ብልግና የሚሆነው ባለጌ ሰው ሲያወራው ነው›› አሰኝተውኛል፡፡ ከነዚያ መካካል አንዱን ብጠቅስ ከጥቂት ዓመታት በፊት “የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አማኞች ተማሪዎች ህብረት” (ኢቫሱ)፤ በኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች ለሚማሩ ተማሪዎች አዘጋጅቶት በነበረው አውደ ጥናት ላይ ታድሜ ነበር፡፡ እጅግ የሚገርሙና በስታቲስቲክስ የተደገፉ መረጃዎችን ያደመጥኩትም እዚያው ነው፡፡
በወቅቱ የወጣቶቹ የአፍላ ዘመን ግፊቶች ይበልጡኑ እንዲጋጋል አስተዋጽኦ ካላቸው የመገናኛ አውታሮች የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው ማህበራዊው ድረ-ገፅ ስለመሆኑ በአውደ ጥናቱ ላይ ሲነገር አድምጬያለሁ። በዚህና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በእውቀትና በእምነት ላይ የተመሠረቱ ሰፊና ጥልቅ ትንተናዎች ሲሰጡ ሰምቼ ብርቱ መደመም ውስጥ ገብቼም ነበር፡፡ በበቀደም ዕለታው የኦባማና የምክር ቤታቸው የውሳኔ አዋጅ መደንገጥ የሚገባኝን ያህል ያልደነገጥኩትም ነገሮች ወዴት እያመሩ እንዳሉ የሚያመላክቱ ብዙ መረጃዎች ቀደም ብለውም መሬቱ ላይ ስለነበሩ ነው፡፡ ውሳኔው በእውነት ላይ ማላገጥ ቢሆንም መልካም አቀባበል እንድናደርግለት ግን ቀደም ብሎ ጭንቅላታችን ላይ አዚሙ ሲደረግ ቆይቷል! አንዳንድ የአውሮፓና የአሜሪካ ቤተ ክርስቲያናት የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን ተቀብለው በመድረኮቻቸው ላይ ማጋባትና ቡራኬ ሰጥተው መሸኘት ከጀመሩ ሰንብተዋል፡፡ በእነዚህ አገሮች የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን መንቀፍ የሰውን ሰብዓዊ መብት በመንካት ወንጀል የሚያስከስስ ከሆነም ቆይቷል፡፡
 እናም በዚያ የወሲብ ጣጣዎችና መፍትሔዎቹ ላይ ለመምከር ታድሞ ለነበረው ጉባኤ፤ “ወሲባዊ ተፈጥሮን መረዳት” በሚል ርዕስ ንግግር ያደረጉት አቶ ንጉሴ ቡልቻ፣ ቀደም ብለው በቀውሱ ውስጥ የገቡ ወጣቶችን ከገቡበት ፈተና ለማውጣት መኬድ ስላለበት መንገድ ሲያወሱ፤  “የወሲብ ሃሳብ ገና ከጨቅላነት ዕድሜ አንስቶ የሚጀምር በመሆኑ ጉዳዩ የማይመለክተው ሰው የለም” ካሉ በኋላ ይልቁንም ካለፉት 40 ዓመታት ወዲህ በአውሮፓ በተቀሰቀሰው የወሲብ አብዮት ምክንያት ብዙዎች ነጋ ጠባ ይህንኑ ብቻ እያውጠነጠኑ ውለው እንዲያድሩ መደረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ ዛሬም ድረስ ይኸው አብዮት መቀጣጠሉን ባለማቆሙ ወጣቶቻችን ነገሩ ካመጣባቸው ወጥመድና የጎንዮሽ ጠንቆቹ ይላቀቁ ዘንድ ብዙ ምክር፣ከብዙ ፍቅር ጋር ሊለገሳቸው እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ “ወጣቶቻችን ልቦና ውስጥ ለሚፈጠሩ ወሲብ ተኮር ጥያቄዎች ምን ዓይነት ምላሽ መስጠት እንደሚገባ በቅጡ ለመምከር እንደህ ዓይነቱ ፕሮግራም መዘጋጀቱ በጣም አስፈላጊና ጠቃሚ ነው” ያሉት አቶ ንጉሴ፤አንድ/አንዲት ወጣት አእምሮ ውስጥ “ከጋብቻ በፊት ወሲብ ብፈጽምስ?”፣ “ከተመሳሳይ ጾታዬ ጋር የወሲብ ፍላጎት ቢያድርብኝስ?”፣ “ሳልፈልገው የመጣብኝን ጽንስ ባስወጣውስ?”፣ “ስለ ወሲብ የተጻፉ ጽሁፎችን ለማንብብ ብገፋፋስ”፣”ወሲብ ቀስቃሽ ምስሎችንና ፊልሞችን የመመልከት ፍላጎት ቢያድርብኝስ?” ለሚሉና የመሳሳሰሉት ጥያቄዎች በዋናነት መለኮታዊ ምላሾቻቸውን ማቅረብ የሚገባም ቢሆን እነዚህን ለመሳሰሉት የወጣቶች ግርታን የተሞሉ ጥያቄዎች ምላሽ በሚሰጥበት ጊዜ በእውቀት ላይ የተመሠረተ፣ ፍቅር፣ ርህራሄና ብልሃት ያልተለየው አቀራራብ እንደሚያስፈልግ በአጽንኦት አሳስበዋል፡፡  
ብልህ መካሪ አያሳጣን!
በአገራችን “መካሪ አያሣጣህ!” የሚል የምርቃት ቃል አለ፡፡ እነሆ ከላይ በተዘረዘረው መልኩ መልካም መካሪና ዘካሪ የሚያገኙ ወጣቶችም ዕድለኞች ናቸው። በወጣትነት ዘመን ላይ ከሚከሰተው ጠንካራ የወሲብ ፍላጎትና የአቻ ግፊት ባሻገር በዚህ ዘመን ላሉ ወጣቶችና ታዳጊዎች ብርቱ ፈተና የሆነው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂው መስፋፋትና እኩዩም ሆነ ሰናይ መረጃዎች በቀላሉ የመገኘታቸው ጉዳይ ነው፡፡  የብዙዎች አፍላ ወጣቶቻችን አካላዊ ስሜት ገደቡን ጥሶ ወደ ተሳሳተ ተግባር እንዲገቡ እያደረገ ያለውም በዚሁ ቴክኖሎጂ በኩል እየሾለኩ የሚመጡት የተሳሳቱ መረጃዎች ናቸው። ዛሬ ላይ የብዙ ወጣቶችና ታዳጊ ልጆች መካሪና ዘካሪዎችም እነዚሁ ናቸው፡፡ በተለይም በዚህ ቴክኖሎጂ አንድ ፈርጅ ውስጥ ተፈጥሯዊ ግፊቶቻቸውን በቀላልና ርካሽ በሆነ መንገድ እንዲያሰክኑት የሚያበረታቱ ትምህርቶችን የሚያገኙባቸው ብዙ ሀዲዶች ተዘርግተውላቸዋል፡፡ የአፍላነት ዘመን ፍላጎቶቻቸውን ግለት ተግነው ግዳያቸውን ሊጥሉ ባደቡ ብዙ አዳኞችም ተከብበዋል፡፡    
የዛሬ አምስት ወይም ስድስት ዓመት ገደማ አሁን በህትመት ላይ የሌለችው የ”አዲስ ነገር” ጸሃፊ አህመድ ሰልማን፤ ምስል ከሳች በሆነው ግሩም አጻጻፉ “የታዳጊዎቹ ኢሮዬቲክ ፓርቲ” በሚል ርዕስ ይዞት የወጣው ዘገባ በወቅቱ ብዙ ወላጆችን ያስደነገጠና ያሸማቀቀ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ሁሉን ቃል በቃል ላሰፍረው ባልችልም ከብዙ በጥቂቱ ግን የሚከተለውን ይመስላል፡፡ 12ኛን ክፍል ማጠናቀቃቸውን ምክንያት ያደረጉ አዲስ አበባ የሚገኘው “ናዝሬት ትምህርት ቤት” ታዳጊ ሴት ተማሪዎች ቦሌ መዲሃኒዓለም አካባቢ በሚገኝ አንድ “ላውንጅ” ውስጥ ፓርቲ አዘጋጅተዋል፡፡ እነዚህ ታዳጊ ሴት ልጆች በፓርቲያቸው ላይ እንዲታደሙ ግብዣ ያደረጉላቸው ወንድ ታዳጊዎች ደግሞ “ቅዱስ ዮሴፍ” እና “ካቴድራል” በመባል በሚታወቁት ሁለት ትምህርት ቤቶች የሚማሩ እኩያዎቻቸው ናቸው፡፡
የጋዜጣው ዘጋቢ በሥፍራው ተገኝቶ እንደተመለከተው፣ አብዛኞቹ ልጃገረዶች የለበሷቸው ልብሶች ሰውነታቸውን አጋልጠው የሚያሳዩ፣ ለብሰውም “ራቁታቸውን” እንደሆኑ እንዲሰማን የሚያደርጉ ስለመሆናቸው ይገልጻል፡፡ ሆቴሉ ደጃፍ ላይ ቆመው ለክብር እንግዶቻቸው የ”እንኳን ደህና መጣችሁ” አቀባበል የሚያደርጉት ጥቂት ታዳጊ ቆነጃጅት እድሜያቸውን በማይመጥኑ አልባሳት ተሸላልመው የመጡ ወንድ እንግዶቻቸውን ወደ ውስጥ የሚሸኟቸው ከንፈሮቻቸውን እየሣሙ መሆኑም ፈጽሞ ያልተለመደና ዕንግዳ ነገር ነበር፡፡ እንደ ጋዜጣው ዘጋቢው እማኝነት ከሆነ፣ አንድ ታዳጊ ወንድ ወደ ውስጥ ከመዝለቁ በፊት በአማካኝ የሦስት ልጃገረዶችን ከንፈር የመሣም ዕድል ነበረው፡፡
እነሆ ፓርቲው እየተጋለለ በሄደ ሰዓት ታዳጊዎቹ ደስታቸውን በዳንስ፣ ሲጋራ በማጨስና አልኮል በመጎንጨት የሚያጣጥሙት ከመሆኑ አልፎ በየጥጋጥጉ ይካሄዱ የነበሩት ትእይንቶች ዘጋቢውን “የት ነው ያለሁት?” የሚያሰኙ ነበሩ፡፡ ዘግየት ብሎም በዚያ “ጫካ” ውስጥ በእነዚያ ታዳጊዎች መካከል ይኖራል ብሎ ያልገመተውን ሌላም ነገር ተመልክቷል። ይኸውም ልዩ ክፍያ በሚጠይቀው የላውንጁ ሌላኛ ጓዳ ውስጥ ለዚያው ተግባር ተብሎ መድረኩ መሃል በተተከለ ምሰሶ ላይ ራቁቷን እየሾረችና የተለያዩ ወሲብ ቀስቃሽ እንቅስቃሴዎችን እያሳየች የታዳጊዎቹን አቅል የምታስት ሴትም ተዘጋጅታ ነበር፡፡ እንግዲህ፣ እንዲህ ባለው የአፍላነት እድሜ በዚህ ዓይነቱ ልምምድ ውስጥ ለመገኘት ትምህርቱ የተቀሰመበት ቦታና ሁኔታ መኖሩ ግልጽ ነው፡፡ ለእነዚህ ታዳጊዎች ድርጊት መነሻ የሆኑ መረጃዎች በአመዛኙ የሚገኙትም ፖርኖግራፊክ (ወሲብ ቀስቃሽ) የሆኑ መልእክቶችን በያዙ ድረ-ገጾች፣ መጽሔቶችና ፊልሞች መሆኑም አጠያያቂ አይደለም፡፡
በዚህ ዘመን ከትልልቆቹ ባልተናነሰ ሁኔታ ትንንሾቹም ልጆች ገብተው የሚጠፉበት ጥቅጥቁ ጫካ ፖርኖግራፊ መሆኑ ከታወቀ ሰነባብቷል፡፡ ለዚህ ምሳሌ የሚሆነኝ ሁለተኛው ማሳያዬም ምናልባት ከሁለት ዓመት በፊት በዚሁ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በመታሰቢያ ካሳዬ ተጽፎ ያነበብኩት የሁለት ታዳጊ ወንድም እና እህት ታሪክ ነው፡፡ የእነዚህ ታዳጊ ልጆች ወላጆች በሥራ የተጠመዱና አብዛኛውን ጊዜ ቤታቸው የማይገኙ ባተሌዎች ናቸው፡፡ ሆኖም ልጆቻቸው ሰርክ ከትምህርት ቤት ወደ ቤት እንጂ ሌላ ነገር የማያውቁ ጨዋዎች አድርገው ነው የሚቆጥሯቸው፡፡ በሌላም በኩል አደራ በሰጧት የቤት ሠራተኛቸው ላይ እምነታቸውን ጥለው በዚያም እረፍት ሲሰማቸው ቆይቷል፡፡ ከዕለታቱ በአንደኛው ቀን የተፈጠረው አስደንጋጭ ክስተት ግን ነገር ዓለሙን ሁሉ አደበላለቀው፡፡
ከክስተቱ በኋላ የቤት ሠራተኛዋ ለፖሊስ በሠጠችው ቃል፣ ልጆቹ ሁልጊዜም ቤት በሚውሉበት ወቅት አቅራቢያቸው ከሚገኝ ቪዲዮ ቤት እየተከራዩ የሚያመጧቸው ፊልሞች እንደነበሩ ገልጻ፣ፊልሞቹ ጤናማ ያልሆኑ ትዕይንቶችን የያዙ መሆናቸውን ግን በጭራሽ እንደማታውቅ ተናግራለች፡፡ ያቺ ምስኪን የቤት ሠራተኛ ሁሉም ነገር የተገለጠላት ከዕለታቱ በአንደኛው ቀን ከዚህ ቀደም ሰምታው የማታውቀውን የጩኸት ድምፅ ሰምታ ልጆቹ ወደነበሩበት ክፍል በገባችበት ሰዓትና የወንዱን ልጅ የተራቆተ ሰውነት፣ መርበትበትና ድንጋጤ  ከሴቷም ልጅ የመራቢያ አካል አካባቢ የሚፈሠውን ደም ባየችበት ቅጽበት ነው፡፡ ያኔም የድረሱልኝ እሪታዋን ታቀልጠዋለች፡፡ የልጆቹ የኋላ ታሪክ ከተጠና በኋላ ዘግይታ የሰማችው ሀቅ ለካስ እነዚያ የአደራ ልጆቿ በፀጥታ ተውጠው ሲኮመኩሙ የሚውሉት የወሲብ ፊልም ኖሯል፡፡ ያን ዕለትም ቢሆን  ድንገት እህትና ወንድም መሆናቸውን አስረስቶ በዚያ አይነቱ ፈተና ውስጥ እንዲወድቁ የገፋፋቸው እሱው ነበር፡፡
ሌላም የባሰ ነገር በማህበረሰባችን ውስጥ ሰፍኗል!
ዳንኤል ክብረት ሰኔ 2005 ዓ.ም ላይ በወጣው “አዲስ ጉዳይ” መጽሔት፤ “ወላጆች፡-ሁለት ጉዳዮች አሉኝ” በሚል ርዕስ ያሰፈረው ጽሁፍ ሌላም የባሰ ነገር በማህበረሰባችን ውስጥ እየሰፈነ መምጣቱን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ “ባለፈው ሰሞን አንዲት እናት ወደ ቢሮዬ መጥተው እንዲህ አወጉኝ፡፡” የሚለን ዳንኤል ክብረት፤ተጠቃሽዋ እናት የነገሩትን እንዲህ ይተርክልናል፡- “ልጄ የአሥራ ሁለት ዓመት ልጅና የ5ኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡ አልፎ አልፎ የማይበት ጠባይ ግራ የሚያጋባኝ እየሆነ ተቸግሬ ነበር፡፡ ወደ ትምህርት ቤት ሲሄድ የእኔን ሽቱ ይቀባል፡፡ እኔም ይሄን ሳይ የልጅ ነገር አድርጌ ትቼው ነበር፡፡ በኋላ ግን ከሌላው ነገር ጋር ሲደመርብኝ ነው ግራ የተጋባሁት፡፡ ፀጉሩን እንደ ሴቶች ማስተኛት ይፈልጋል፡፡ ጥብቅ ያለ ሱሪ ካልገዛሺልኝ ይለኛል፡፡ አንድ ቀን ትምህርት ቤት አድርሼው መኪናዬን አዙሬ ልመለስ ስል ከኋላ ያለውን መኪና እንዳልነካው ዞር አልኩ፡፡ ያን ጊዜ ያየሁትን ነገር ዓይኔ ሊያምን አልቻለም፡፡ ከሌላ አንድ ወንድ ልጅ ጋር ከንፈር ለከንፈር ሲሳሳሙ አየኋቸው፡፡ ከኋላ የነበረው መኪና በጡሩምባ እየጮኸብኝ እንኳ የማየውን ተጠራጥሬ ለረዥም ሰዓት ፈዝዤ ነበር፡፡” የሚሉት እኚህ እናት፤አንድ ሁነኛ ሰው ካማከሩ በኋላ ያደረጉትን ደግሞ እንዲህ ሲሉ ለዳንኤል ያወጉታል፡-
“አንድ ቀን አባቱ ወደ መዝናኛ ቦታ እንዲወስደው ነገርኩትና እኔ እቃዎቹን መፈተሸ ጀመርኩ፡፡ ያኔ ነው የልጄን ጉዳይ በጥልቀት የተረዳሁት፡፡ እኔ ያልገዛሁለትን አንድ ቀይ ቲሸርት አገኘሁ፡፡ ቲሸርቱ ላይ በእንግሊዝኛ “I am a gay” የሚል ተጽፎበታል። እንባዬን መቆጣጠር አልቻልኩም፡፡ አልጋው ላይ ተቀምጬ ለረዥም ሰዓት አለቀስኩ፡፡ ከዚያ በኋላ ልጄን እንዳጣሁት ገባኝ፡፡ ልጄን እንደማላውቀው ገባኝ። ልጄና እኔ በተለያዩ መንገዶች እየተጓዝን መሆኑ ገባኝ።” በማለት የደረሰባቸውን ጠሊቅ ሀዘን ያጫውቱታል። የዳንኤል ክብረት ጽሁፍ ጭብጥም ቢሆን “ወላጆች ሆይ ልጆቻችሁን ምን ያህል ታውቋቸዋላችሁ?” የሚል ከንካኝ ጥያቄ በመጠየቅ ወላጆችን ማንቃት ነበር፡፡ ነገሩን በእንጥልጥል ላለመተው ያህል ግን እኚያ እናት በብዙ ብልሃት ልጃቸውን አግባብተው እውነቱን እንዲነግራቸው በጠየቁት ሰዓት ልጁ፤ “እማዬ እኔኮ ጌይ ሆኛለሁ!” እንዳላቸው፣እነርሱ ትምህርት ቤት እንደዚያ የሆኑ ብዙ ልጆች ስለመኖራቸው፣” I am a gay” የሚል ቲሸርት እንደሚለብሱ፣አንድ አይነት ማስቲካ እንደሚያኝኩ፣ በዕረፍት ሰዓታቸው ላይ አንድ ጓደኛቸው (ይኸውም የልጃቸውን ከንፈር ሲስም ያዩት መሆኑን ልብ ይሏል) በሞባይሉ የጌይ ፊልሞችን እየጫነ እየመጣ እንደሚያሳያቸው፣ ይህንን የምታደርግለት እናቱ እንደሆነች፣ አባቱም ሁሌ ሲሸኘው ከንፈሩን እንደሚስመው… ሁሉንም ዝርዝር አድርጎ እንደነገራቸው ለዳንኤል ገልጸውለታል፡፡  
 እየበረታ የመጣው የወላጆች ሥጋት
ለእኔ ደግሞ ቀጣዩን መረጃ ያቀበለችኝ አንዲት ስለ ልጆቿ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ሠርክ በመጨነቅ ላይ ያለች እናት ናት፡፡ ይህች እህቴ ዘጠኝ ወራት በሆዷ ተሸክማና አምጣ የወለደቻቸው ሦስት እንቦቃቅላዎቿ የዚህ ክፉ ዘመን እኩይ ልምምዶች ሰለባ እንዳይሆኑባት በመስጋት ገና ከአሁኑ እንደምን እንደ ቆቅ ነቅታ እንደምትጠባበቃቸው የነገረችኝ ዕለት በሥጋቷ ሳይሆን ጥበቃ በምታደርግበት ስልት ከት ከት ብዬ ስቄያለሁ። (ያልተነካ… እንዲሉ) በአንፃሩም በዚህ ዘመን ያሉ ወላጆች ሸክም እንደምን እየከበደ እንደመጣ አመላክቶኝ ከልቤ አዝኛለሁ፡፡
የዚህችን እህት የወትሮ ሥጋት ይበልጡኑ ያባባሰው ጉዳይ እንድመለከተው ባዋሰችኝ DVD ውስጥ ይገኛል፡፡ DVDው አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት ውስጥ የተከናወነ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዐውደ ጥናት ተቀርጾ የተቀመጠበት የመረጃ ማኖሪያ ቋት ነው፡፡ DVDውን ላፕቶፔ ውስጥ ጨምሬ መዝግቦ የያዛቸውን ትዕይንቶች ስመለከት፣ አሁን በዚህ ጋዜጣ ላይ ልጽፋቸው የማልችላቸውን ጨምሮ ብዙ የሚገራርሙ የዘመናችንን ነውረኛ ታሪኮች ለመታዘብ ችያለሁ፡፡ በዐውደ ጥናቱ ላይ ዶ/ር ስዩም አንቶኒዮስ፣ “ማየት” ከሰው ልጆች ጋር ያለውን ትስስርና ትውልዱ ከፊልም ጋር እንዴት እንደተቆራኘ ሲያስረዱ፤ “seeing is actually doing when it comes to how our brains work” የሚለውንና ማየት የድርጊትን ያህል ስለሚሆንበት ሁኔታ የሚያብራራውን አንድ በቅርቡ ይፋ የተደረገን የሳይንሳዊ ምርምር ግኝት ዋቢ አድርገዋል፡፡
“የዘመኑ ልጆች የፊልም ልጆች ናቸው” ያሉት ዶክተሩ አክለውም “ልጆቻችን ከእኛ ከወላጆቻቸው ይልቅ ቅርበታቸው ከፊልም ጋር ስለሆነ አስተሳሰባቸውን የምንቀርጸው እኛ ሣንሆን በፊልም ውስጥ የሚመለከቷቸው ገፀ ባህሪያት ናቸው” ይላሉ፡፡ በሰከንዶች ሽርፍራፊ ውስጥ በልጆች አይን በኩል ወደ አእምሯቸው የሚዘልቁ ትዕይንቶች ለዘመናት የማይረሱ ትውስታዎች ሆነው እንደሚዘልቁም ሌሎች ሳይንሳዊ ዋቢዎችን በመጥቀስም አስረድተዋል፡፡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዐውደ ጥናቱ በዋናነት ካተኮረባቸው ጉዳዮች መካከል የተመሳሳይ ጾታ ወሲባዊ ፍላጎትና ፖርኖግራፊ ዋነኞቹ ነበሩ፡፡  
አንድ ሰው የፖርኖግራፊ ሱሰኛ ለመሆን የሚያበቃው የዕይታ ጊዜ የአንድ ሴኮንድ 1/3ኛ እንደሆነ የገለፁት ዶ/ር ስዩም፤ ልጆች ለሚመለከቷቸው የፊልም ትእይንቶች ወላጆች ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡ “በዚህ ዘመን ልጆቻችን የሚያነቧቸው መጽሔቶች አስደንጋጭ ናቸው” ያሉት ዶክተሩ፣ ብዙ ታዳጊ ልጆች ወሲባዊ ምስልን በግልፅ የሚያሣዩ ገፆች ያሏቸውን እንደ  “Play boy” የመሳሰሉትን  መጽሔቶች መዋዋስ ከጀመሩ መሰነባበታቸውን ጠቅሰው ዛሬ ላይ እንዲህ ዓይነት ፖርኖግራፊክ የሆኑ ምስሎችንና ቪዲዮዎችን በስልኮቻቸው መቀባበል በእነርሱ ዘንድ ትልቅ ነገር አለመሆኑንም በታላቅ የሀዘኔታ መንፈስ ገልጸዋል፡፡
“ኢንተርኔት ዋናው የልጆቻችን መጥፊያ መንገድ ሆኗል!” ያሉት ዶ/ር ስዩም፤ የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ ምንም እንኳ በራሱ እጅግ ጠቃሚ የሆነ የመገናኛ አውታርና የብዙ እውቀቶች ማግኛ ድልድይ ቢሆንም አብዛኞቹ ልጆች ግን በአመዛኙ የሚጠቀሙበት ለመጥፊያቸው የሚሆነውን ፖርኖግራፊ ለመመልከቻነት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ “እኛው ራሣችን በውድ ዋጋ ገዝተን በምንሰጣቸው የእጅ ስልኮቻቸው በቀላሉ ዘው ብለው የሚገቡበት የመረጃ መረብ (ጫካ) በሚዘገንን ሁኔታ ለህፃናት ተብለው ወደሚዘጋጁ የፖርኖግራፊ ሳይቶች ነው” ያሉት ጥናት አቅራቢው፤ በአንድ ት/ቤት  የሆነውን ታሪክ በምሳሌነት ሲያወሱም፣ አንድ ታዳጊ ልጅ በሞባይሉ ላይ ጭኖ ያመጣውን የህፃናት ፖርኖግራፊ ሌሎች አራት ጓደኞቹን ጠርቶ እያሣያቸው ሣለ ድንገት የደረሠባቸው መምህር እንዳጫወታቸው ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር ስዩም “አዲሱ ሃይማኖት” ብለው የሚጠሩት ፌስ ቡክ  የተሰኘው ማህበራዊ ድረ ገፅም ቢሆን ብዙ ወጣቶች በቀን ሁለትና ሦስት ጊዜ ሳይሳለሙት የማይውሉት ጣኦት እየሆነ መምጣቱን ገልፀው፣ ድረ ገፁ በራሱ ያለው ጠቀሜታ  ባይታበልም በቀን አምስትና ስድስት  ሰዓት እዚያ ላይ ተጥዶ የሚዋልበት ምክንያት ግን በአመዛኙ ሌላ መልክ ያለው እንደሆነ አመላክተዋል። “ፌስ ቡክ ላይ ብዙ ጥሩ ነገሮችን ተመልክቼ አውቃለሁ፡፡” ያሉት ዶክተሩ፤ ሆኖም ከተጠቃሚዎቹ አብዛኛዎቹ ነገሩን የሚጠቀሙበት ለወሬና ለፖርኖግራፊ መቀባበያነት እንደሆነ አውስተዋል፡፡ “Daily mirror”  የተሰኘው ታዋቂ መጽሔት እ.ኤ.አ በ2012 “sex” የሚለውን ቁልፍ ቃል በመጫን  ቀዳሚ እንደሆኑ ከጠቀሷቸው አገሮች መካከል (Top of nation in sex search in Google) ኢትዮጵያ ቀዳሚውን ሥፍራ መያዟም የገባንበትን ቀውስ አመላካች አድርገው አቅርበውታል፡፡  
“እንዲያምን አድርገው!”
ማንኛውም የፈጠራ ሥራ መመዘን ያለበት በውስጡ ከያዘው መልእክት አንፃር መሆን እንዳለበት አምናለሁ፡፡ በገሃዱ ዓለም እውነታዎች የበለጠ ጎልተው ከሚታዩበት የጥበብ ዘርፍ አንደኛውም ፊልም ነው። እንደየሁኔታው በዚያ ውስጥ የሰዎች እምነት፣ ባህል፣ የአስተሳሰብ ሥርዓትና የህይወት ፍልስፍና ይንፀባረቃል፡፡ ፊልም እንደ ሌሎች የኪነ ጥብብ ፈርጆች ሁሉ ማህበራዊ እሴቶች የሚጎሉበት አሊያም እንደ ገለባ ቀለው የሚታዩበት መስክ ነው፡፡ ከዛሬው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ማደግና መንሠራፋት የተነሣ፣ ከየትኛውም ዘመን ይልቅ የተለያየ ባህልና እምነት ያላቸውን ህዝቦች በአንድ ዓይነት የአመለካከትና የስሜት ቦይ ውስጥ እንዲፈስሱ ከሚገደዱባቸው መሣሪያዎች ዋነኛው ፊልም ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡
ይህ ዓይነቱ የአስተሳሰብ መንጋነት ለሰናይ ዓላማ ሆኖ ቢሆን መልካም ነበር፡፡ አሳዛኙ ግን ተቃራኒው መሆኑ ነው፡፡ ዴቪድ ሪስማን የተሰኘ አሜሪካዊ የሥነ - ህብረተሰብ ባለሙያ ይህን አስመልክቶ ሲፅፍ፤ “የሃያኛው ምዕተ ዓመት ግለሰቦች ህይወትን የጠሉ፣ ዓላማ የሌላቸው፣የመወስን ድፍረት የጎዳላቸው፣ ተጨባጭ እውነታን ለመገምገም የማይችሉና የሰጧቸውን ሁሉ በዘፈቀደ የሚቀበሉ ህያው አሻንጉሊቶች ናቸው” ማለቱም እውነታውን ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡ የአሜሪካ ህዝብ የሚመራው ከነጩ ቤት (ኋይት ሃውስ) በሚወጣው ህግ ሣይሆን በሆሊዉድ ምናብ ስለመሆኑ መነገሩም ያለ ምክንያት ዓይደለም፡፡ ሰሞነኛውም የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ ህጋዊነትም ቢሆን ከነጩ ቤት ይነገር እንጂ ምንጩ ሆሊ ዉድ እንደሆነ ብዙዎች ያምናሉ፡፡
በፊልሞች ውስጥ የሚንፀበራቀው ሃሳብ ነው። ከታሪኩም ቢሆን ሠፊውን ቦታ የሚይዘው ሃሳብ ነው፡፡ ሃሳብ የማይጨበጥ ቢሆንም ተጨባጭ ነገሮችን በውስጣችን ይፈጥራል፡፡ የሰው ልጅ ሃሳብና ገሃዳዊው ዓለም የተቆራኙ በመሆናቸው ልጆች ብቻ ሳይሆኑ በሁሉም የእድሜ ክልል ያሉ ሁሉ በፊልም ውስጥ ስለ ሚመለከቷቸው ታሪኮችና ጭብጦች ተገቢውን ጥንቃቄና ምርመራ ማድረግ እንደሚገባቸው የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ የኪነ ጥበብ ባለሙያው በላይነህ አቡኔ “ፈርጥ” በተሰኘች የኪነ ጥበብ መጽሔት ላይ (1995) “ሆሊውድ አዝናኝ ኢንዱስትሪ ወይስ…?” በሚለው ጥርጣሬ አዘል ፅሁፉ፤ ፊልም የዘመናችን ኃያልና ተወዳዳሪ የሌለው የጥበብ ዘርፍ እንደሆነ ጠቅሶ፣ ለአንድ የፊልም ዝግጅት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ገንዘቦች ለምን እንደተራ ነገር እንደሚወጡ መጠየቅ የብልህ ሰው ጥያቄ መሆኑን ይገልፃል፡፡ “አዝናኝ” ከሚባሉት ፊልሞች በስተጀርባ ያለውን “ስውር አጀንዳ” ወይም “ርዕዮተ ዓለማዊ” ተልዕኮ መፈተሽና መመርመር እንደሚገባም ይመክራል፡፡
በላይነህ አቡኔ በዚህ ጽሁፉ፤ “የሆሊዉድ ፊልሞችንና የቴሌቪዥን ሶፕ-ኦፔራዎችን በተናጠል ወስዶ በጥልቀት የሚፈትሻቸው ንቁ ተመልካች ቢኖር፣ ከዚያ የሚገነዘበው ሀቅ ፊልሞችም ሆኑ ድራማዎቹ የሠሪዎቻቸውን መደባዊ አስተሳሰብ የሚያንፀባርቁ፣ የሥርዐተ ጾታንና ፖለቲካዊ ተፅእኖዎችን የተላበሱ መሆናቸውን ያውቃል፡፡”
በማለት ገልጾ፣ የሰጡንን ሁሉ እንደወረደ የምንቀበል መሆን እንደሌለብን ያስጠነቅቃል፡፡ እንደ እርሱ እምነት ፈንጆች፤ “Make believed” ወይም “እንደሚታመን አድርገው!” በሚሉት በዚህ ጥበብ በኩል ዓላማቸው እንዲተላለፍላቸው የፈለጉትን መልእክት ሁሉ ለሌሎች አስመስሎ ማሳየትና ማሳመን በመሆኑ፣ ያንን የምር ማጤን ብልህነት እንደሆነ ይገልጻል፡፡ የሳይንስ ልብ ወለድ ጸሐፊው ብሬድበሪ ያለውን ጠቅሶም እንዲህ አይነቶቹን ፕሮፓጋንዳዎች ለመቃወም ያልተዘጋጀ ማህበረሰብ እውነተኛውን ጦርነት በቴሌቪዥን ሳይሆን ገሃድ በሆነ የጦር ሜዳ ሊያየው እንደሚችል ያስጠነቅቃል፡፡  

Published in ጥበብ

ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ አቅምና ጡንቻ ላላቸው የፋይናንስ ዘርፍ ኢንዱስትሪዎች በሯን እንደዘጋች ነው፡፡ ይህን በቴክኒክ፣ በካፒታል፣ በእውቀት፣ በባንክ አሰራርና በሰው ኃይል አቅማቸው ላልጠነከረውና ላልዳበረው የአገር ውስጥ ባንኮች ከለላ ሆኖ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ከአሁን በኋላ ግን የሚቀጥል አይመስልም፡፡
በቅርብ ዓመታት አገሪቷ የዓለም ንግድ ድርጅት (WTO) አባል እንደምትሆን እየተነገረ ነው፡፡ በፋይናንስ ኢንዱስትሪው የፈረጠመ ክንድ ያላቸው ባንኮች ካፒታል፣ እውቀትና ዓለም አቀፍ ልምድ፣ … ይዘው የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እንደሚቀላቀሉ ይጠበቃል፡፡ በዚያን ጊዜ አገር በቀሎቹ ባንኮች በቀድሞው ሁኔታ መቀጠል አይችሉም፡፡ በዘርፉ የላቀ እውቀትና ልምድ ያላቸው አንዳንድ ባለሙያዎች፣ በኢትዮጵያ ያሉ አንዳንድ ባንኮች ካልተዋሃዱ በስተቀር ለብቻቸው ከግዙፎቹ ባንኮች ጋር መፎካከር አይሆንላቸውም የሚል ሀሳብ እየሰነዘሩ ነው፡፡
አገር በቀሎቹ ባንኮች ይህ ሁኔታ ቢዘገይ እንጂ የማይቀር መሆኑን የተገነዘቡ ይመስላል፡፡ ወቅቱ ሲደርስ ከፋይናንስ ኢንዱስትሪው ተሽቀንጥረው እንዳይወጡ፣ ተወዳዳሪ ሆነው ገበያው ውስጥ ለመቆየትና ከአለም አቀፍ የባንክ አሰራር ጋር ለመላመድ በዘርፉ እውቅና ካላቸው ባንኮች ጋር መስራት ወይም የቀረፁትን የወደፊት ዕቅድን እንዲያስፈፅሙላቸው ወይም የአሰራር እቅድ እንዲቀርፁላቸው … እያደረጉ ነው፡፡
የአገሬው ባንኮች የውጪዎቹ የሚጠቀሙበት ዘመናዊ መሳሪያና ሶፍትዌር ሊገዙ ይችላሉ፡፡ መሳሪያዎቹ ቢገዙም በራሳቸው አይንቀሳቀሱም፡፡ መሳሪያዎቹን የሚተክል፣ ሶፍትዌሮቹን የሚገጥም፤ አሰራራቸውን የሚያውቅና የሚከታተል ክህሎቱ የዳበረ፣ በዘርፉ በሚገባ የሰለጠነ ዓለም አቀፍ የባንክ አሰራር የሚያውቅ ባለሙያ የላቸውም፡፡ እንግዲህ ይህን እጅግ አስፈላጊ የሆነ የሰው ኃይል ለማፍራት እየጣሩ ነው፡፡
በዚህ ረገድ አቢሲኒያ ባንክ አ.ማ በባንክ ኢንዱስትሪው ውስጥ ጥሩ የተወዳዳሪ ሆኖ ለመቀጠልና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን አሰራር ለመዘርጋት፣ እንዲሁም ባንኩ በቀጣይ አምስት ዓመት የሚመራበትን መሪ እቅድ (ስትራቴጂክ ፕላን) ቀርፆ በመተግበር እንዲያማክረው ዓለም አቀፍ የቢዝነስ አማካሪ ለመቅጠር በመወሰን በዓለም ታዋቂ የሆኑ 4 የቢዝነስ አማካሪ ድርጅቶችን አወዳድሮ አሸናፊ ከሆነው ዲሊዮት (Deloitte) ኩባንያ ጋር ለመስራት በሳምንቱ መጀመሪያ በሂልተን ሆቴል ተፈራርሟል፡፡
አማካሪ ድርጅቱ ከሳምንት በፊት ስራውን በይፋ መጀመሩንና በ6 ወራት ውስጥ የስትራቴጂ እቅዱን ሰርቶ ለመጨረስ መስማማቱን የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አስማረ ጠቅሰው፣ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የስተራቴጂውን አፈጻጸም (Organizational Transformation) በቅርበት በመከታተልና በመተግባር እንደሚያማክራቸው ተናግረዋል፡፡
ባንኩ ከዚህ ቀደም 3 የአምስት ዓመት ስትራቴጂዎችን ቀርፆ ተግባራዊ ማድረጉን፣ በባንክ የሥራ ዘርፍ ያለውን ውድድር በብቃት ለመወጣትና ከዘመኑ ጋር በመራመድ ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ አዳዲስ አሰራሮችንና ቴክኖሎጂዎችን በመግዛት በባንክ ኢንዱስትሪው ውስጥ የበኩሉን ሚና ሲያበረክት መቆየቱን የገለፁት ፕሬዚዳንቱ፣ እየሰፋ የመጣውን የባንክ አገልግሎት ፍላጎት ለማርካት፣ በመስኩ ያለውን ውድድር በብቃት ለመወጣት፣ የባንኩን ቀጣይነት ለማረጋገጥ የባለድርሻ አካላትን ፍላጎት በሚገባ ለማርካትና ዘመኑ የሚጠይቀውን የባንክ አሰራር ለመከተል ዲሊዮት እንዲያማክራቸው መስማማታቸውን አስታውቀዋል፡፡
በፊርማው ሥነ - ሥርዓት ላይ የተገኙት የዲሊዮት ኩባንያ ሥራ አስፈፃሚዎች ሁለት ነገር ይዘው መቅረባቸውን ጠቅሰው፣ ኩባንያቸው ኢትዮጵያን ጨምሮ በ6 የምስራቅ አፍሪካ አገሮች የሚንቀሳቀስ በመሆኑ ዓለም አቀፍ የባንክ አሰራር ልምድ እንዳለው፣ በኢትየጵያ ወቅታዊ የባንክ አሰራር ላይ ጥናት በማድረጉ፣ ሁለቱን በማቀናጀትና በቴክኖሎጂ በመታገዝ የደንበኞች አገልግሎት አሰጣጥ እርካታ፣ የባንኩን ዕድገትና የገበያ ተወዳዳሪነት፣ … ለማሳደግ እንደሚሰሩ ገልፀዋል፡፡
አቢሲኒያ ባንክ ከ20 ዓመት በፊት የግል ባንኮች ወደ ኢንዱስትሪው ገብተው እንዲሰሩ በተፈቀደ ማግስት ከተቋቋሙ 3 ባንኮች አንዱ ነው፡፡ 131 ግለሰቦች በከፈሉት የአክሲዮን ድርሻና 18 ሚሊዮን ብር ባልሞላ ካፒታል የተመሰረተው ባንክ፤ በአሁኑ ወቅት  ካፒታሉ 1.5 ቢሊዮን ብር፣ የደንበኞች ቁጥር 462 ሺህ፣ የቅርንጫፎች ብዛት 130 መድረሱንና የባንኩ ተቀማጭ ሀብት ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑ ታውቋል፡፡