ድምፃቸው ጠፍቶ የከረሙት ወጣቶቹ የጃኖ ባንድ የሙዚቃ አባላት ከሚቀጥለው ሳምንትጀምሮ በክለብ H20 ማቀንቀን የሚጀምሩ ሲሆን ለመዲናዋ የመጀመሪያ ነው የተባለውን የሮክሙዚቃ ለታዳሚዎች ያቀርባሉ ተብሏል፡፡ባንዱ ከተቋቋመ ወዲህ በምሽት ክለብ የሙዚቃ ሥራውን ሲያቀርብ የአሁኑ የመጀመሪያውእንደሚሆን ታውቋል፡፡የባንዱ አባላት ሁለተኛ የሙዚቃ አልበማቸውን በሦስት ወራት ጊዜ ወስጥ እንደሚለቁምለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡ከዚህም በተጨማሪ በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች ለ1 ወር የሙዚቃ ኮንሰርት ያቀርባሉ
ተብሏል፡፡ የጃኖ ባንድ አባላት ተለያይተዋል በሚል ሲናፈስ የቆየውን ወሬ መሰረተቢስ ነው
በሚል ባንዱ አስተባብሏል፡፡

- 172 ሴቶች ተጠልፈዋል፣ 79 ሴቶችና ልጃገረዶች ወሲባዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል
- መንግስት ወታደሮቼ ፈጸሙት የተባለውን ድርጊት ለማመን ይከብደኛል ብሏል

     የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የደቡብ ሱዳን መንግስት ወታደሮች በአገሪቱ ሴቶችና ልጃገረዶች ላይ ጠለፋ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ግርፋት፣ በቁማቸው በእሳት ማቃጠል፣ ግድያና የመሳሰሉ አሰቃቂ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶችን ፈጽመዋል ማለቱን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኬር ቃል አቀባይ በበኩላቸው፤ ወታደሮቻችን በገዛ ህዝባቸው ላይ ይህን አይነት አሰቃቂ ተግባር ይፈጽማሉ ብለን ለማመን ይቸግረናል፣ ይሄም ሆኖ በሪፖርቱ የቀረቡትን ውንጀላዎች ችላ አንላቸውም፣ ጉዳዩን በጥልቀት መርምረን ተገቢውን እርምጃ እንወስዳለን ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የደቡብ ሱዳን ሴቶችና ልጃገረዶች በአገሪቱ ወታደሮች የሚፈጸምባቸው ኢ-ሰብአዊ ድርጊት እጅግ አሰቃቂ ነው ያለው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ አንዳንዶቹም ተጠልፈው በግዳጅ ከመደፈራቸው ባሻገር፣ በቁማቸው በእሳት እንዲቃጠሉ መደረጋቸውን ደርሼበታለሁ ብሏል- ባለፈው ማክሰኞ ባወጣው ሪፖርት፡፡
በመንግስት ጦርና በአማጽያን መካከል ላለፉት 18 ወራት የዘለቀው የደቡብ ሱዳን ግጭት፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመባባስ ወደ ደም አፋሳሽ ጦርነት ማምራቱንና አገሪቱን የከፋ ቀውስ ውስጥ እየከተታት መሆኑን ዘገባው ጠቁሟል፡፡ ግጭቱ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ በመንግስት ወታደሮች ከ172 በላይ የአገሪቱ ሴቶች መጠለፋቸውንና 79 የሚሆኑ ሴቶችና ልጃገረዶችም ወሲባዊ ጥቃት እንደደረሰባቸው የገለጸው የተመድ ሪፖርት፣ ዘጠኝ ያህል ሴቶችና ልጃገረዶች ተገደው ከተደፈሩ በኋላ በእሳት መቃጠላቸውን ይፋ አድርጓል፡፡
115 የአይን እማኞችንና የጥቃት ሰለባዎችን እማኝነት በመጥቀስ በደቡብ ሱዳን የተመድ ልኡክ ያወጣው ሪፖርት እንዳለው፣ በአገሪቱ መንግስት ወታደሮች እየተፈጸመ የሚገኘው ጥቃት እየተባባሰ ወደ አሰቃቂ ደረጃ ተሸጋግሯል፡፡ ሱዳን ትሪቢዩን በበኩሉ፤ የመንግስት ጦርና የአማጽያኑ ወታደሮች የአገሪቱን ዜጎች ብሄርን መሰረት አድርገው እንደሚገድሉና መንደሮችን በአሰቃቂ ሁኔታ እንደሚያቃጥሉ በሪፖርቱ መገለጹን ዘግቧል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

አወዛጋቢው የብሩንዲ ምርጫ ባለፈው ሰኞ መካሄዱን ተከትሎ ባለፈው ረቡዕ በመዲናዋ ቡጁምቡራ በተቀሰቀሰ ግጭት አንድ የፖሊስ መኮንንን ጨምሮ ስድስት ሰዎች ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውን ቻናል አፍሪካ ዘገበ፡፡
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ፔሪ ንኩሩንዚዛ ህገ መንግስቱ ከሚፈቅድላቸው ውጪ ለሶስተኛ ዙር በምርጫ ለመወዳደር መወሰናቸውን የተቃወሙ ዜጎች ለወራት የዘለቀ ግጭት ሲፈጥሩ የቆዩ ሲሆን፣ የምርጫ ውጤቱ ይፋ ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቅበት ባለፈው ረቡዕም ከፖሊስ ጋር መጋጨታቸውን ዘገባው ገልጧል፡፡
17 ያህል የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ራሳቸውን ባገለሉበት የሰኞው ምርጫ ድምጽ ለመስጠት የተመዘገበው ህዝብ ብዛት 3.8 ሚሊዮን እንደነበር የጠቆመው ዘገባው፣ ይህም ሆኖ በመዲናዋ ቡጁምቡራና በአካባቢዋ ድምጹን የሰጠው ህዝብ ቁጥር አነስተኛ ነበር ብሏል፡፡ የምርጫው ድምጽ ቆጠራ ባለፈው ማክሰኞ መጠናቀቁን የአገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
ለወራት በዘለቀው ግጭት ከ70 በላይ የአገሪቱ ዜጎች ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

 ባለፉት ስድስት ወራት 137
ሺህ ስደተኞች አውሮፓ ገብተዋል
- በባህር ጉዞ የሞቱ ስደተኞች
ቁጥር ከሶስት እጥፍ በላይ ጨምሯል

   ባለፉት ስድስት ወራት አፍሪካን ጨምሮ ከተለያዩ የአለማችን አገራት በመነሳት የሜዲትራኒያን ባህርን አቋርጠው ወደ አውሮፓ የተጓዙ ስደተኞች ቁጥር በታሪክ ታይቶ በማይታወቅበት ደረጃ ላይ መድረሱንና በስደት ጉዞ ላይ ሳሉ ለህልፈተ ህይወት የተዳረጉ ስደተኞች ቁጥርም ከሶስት እጥፍ በላይ መጨመሩን ሲኤንኤን ዘገበ፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ያወጣውን ሪፖርት ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ ባለፉት ስድስት ወራት የሚዲትራኒያን ባህርን አቋርጠው ወደ ግሪክ፣ ጣሊያን፣ ማልታ እና ስፔን የገቡ ስደተኞች ቁጥር 137 ሺህ የደረሰ ሲሆን ይህም ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅና አዲስ ክብረወሰን ያስመዘገበ ነው፡፡
አብዛኞቹ ስደተኞች ጦርነትና የእርስ በእርስ ግጭት ያለባቸው አገራት ዜጎች መሆናቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ በተጠቀሰው ጊዜ ባህር አቋርጠው ወደ ጣሊያንና ግሪክ ከገቡት ስደተኞች መካከል አንድ ሶስተኛ የሚሆኑት በጦርነት የምትታመሰዋ ሶርያ ዜጎች እንደሆኑ ገልጧል፡፡ ከሶርያ በመቀጠል የበርካታ ስደተኞች መነሻ የሆኑት አገራት፣ በግጭት ውስጥ ያለችው አፍጋኒስታንና ጨቋኝ ስርዓት የገነነባት ኤርትራ ናቸው ያለው ሪፖርቱ፣ ወደ አውሮፓ የሚሰደዱ በርካታ ስደተኞች መነሻ የሆኑት ሌሎች አገራትም ሶማሊያ፣ ናይጀሪያ፣ ኢራቅና ሱዳን መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡
የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ሃላፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስም እንደገለጹት፣ አብዛኞቹ ስደተኞች ወደ አውሮፓ የሚጓዙት የተሻለ ኑሮን ፍለጋ ሳይሆን በአገራቸው ያለውን ግጭት፣ ጦርነትና ስቃይ ለመሸሽና ህይወታቸውን ለማዳን በማሰብ ነው ብለዋል፡፡ ባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ወደ አውሮፓ የገቡ የተለያዩ አገራት ስደተኞች ቁጥር 75 ሺህ እንደነበር ያስታወሰው የተመድ ሪፖርት፣ ይህ ቁጥር ባለፉት ስድስት ወራት የ83 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 137 ሺህ ደርሷል ብሏል፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት የሜዲትራንያን ባህርን አቋርጠው ወደ አውሮፓ ለመግባት ሲሞክሩ ለህልፈተ ህይወት የተዳረጉ ስደተኞች ቁጥር፣ ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከሶስት እጥፍ በላይ ጨምሯል ያለው የተመድ ሪፖርት፣ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 1ሺህ 867 ስደተኞች መሞታቸውን አስታውቋል፡፡
ባለፉት ሁለት ወራት ጣሊያን 67 ሺህ 500፣ ግሪክ 68 ሺህ ስደተኞችን እንደተቀበሉ የጠቆመው ሪፖርቱ፣ የስደተኞቹ ቁጥር  በቀጣዮቹ ስድስት ወራትም በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክቷል፡፡


Published in ከአለም ዙሪያ

- የተናዘዙት ኃጢያት ለሸክም አይከብድም፡፡
የህንዶች አባባል
- ሃዘንህ ከጉልበትህ ከፍ እንዲል አትፍቀድለት፡፡
የስዊዲሽ አባባል
- ወጣትነት በየቀኑ የሚሻሻል ጥፋት ነው፡፡
የስዊዲሽ አባባል
- የተረታ ሰው የተሰጠውን አሜን ብሎ ይቀበላል፡

የሰርቢያኖች አባባል
- ምሳሌያዊ አባባሎች የታሪክ ቤተ መፃህፍት
ናቸው፡፡
የቤልጂየሞች አባባል
- ማንንም እንዲያገባ ወይም ወደ ጦርነት እንዲሄድ
አትምከር፡፡
የዳኒሽ አባባል
- እንቁላልና መሃላ በቀላሉ ይሰበራሉ፡፡
የዴኒሽ አባባል
- በባህር ላይ ሃብታም ከመሆን ይልቅ በመሬት
ላይ ድሃ መሆን ይሻላል፡፡
የዴኒሽ አባባል
- አንደኛው እጅ ሲገነባ፣ ሌላኛው ያወድማል፡፡
የኢራቃውያን አባባል
- የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም፡፡
የኢራቃውያን አባባል
- እናት ስትሞት፣ ጎጆውም ይሞታል፡፡
የኢራቃውያን አባባል
- ውበት የሴቶች ጥበብ ነው፡፡ ጥበብ የወንዶች
ውበት ነው፡፡
የቻይናውያን አባባል
- የቅፅበት ንዴትን ከታገስክ የ100 ቀናት ሃዘንን
ታመልጣለህ፡፡
የቻይናውያን አባባል
- አይጦችን ለማጥፋት ቤትህን አታቃጥል፡፡
የአረቦች አባባል
- መሸለም ቢያቅትህ ማመስገን አትርሳ፡፡
የአረቦች አባባል
- ፀሐይ ምንጊዜም ቢሆን መጥለቋ አይቀርም፡፡
የአረቦች አባባል
- ልጆች የሌሉበት ቤት መቃብር ነው፡፡
የህንዶች አባባል
- ከአዲስ ሃኪም የቆየ በሽተኛ ይሻላል፡፡
የህንዶች አባባል



Published in ከአለም ዙሪያ

በሴቶች 5ሺ 7 አመት የቆየ ሪከርድ ሊሰበር ይችላል

ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር (አይ.ኤ.ኤ.ኤፍ) በ2015 እኤአ የሚያካሂደው ዳይመንድ ሊግ ዘንድሮ በውድድሩ ታሪክ 6ኛው ሲሆን በ14 ከተሞች በዙር የሚካሄደው ውድድሩ በፈረንሳይቷ ከተማ ይጋመሳል፡፡
ተሳታፊ ከሆኑት የኢትዮጵያ አትሌቶች ከፓሪስ ሴንት ዴኒስ የዙር ውድድር በፊት፤ በ5ሺ ሜትር ወንዶች ሃጎስ ገብረህይወት እንዲሁም በ5ሺ ሜትር ሴቶች ገንዘቤ ዲባባ እንደ ቅደም ተከተላቸው ነጥቦች አስመዝግበው እየመሩ ናቸው፡፡
በፈረንሳይ ከተማ በሚቀጥለው ዳይመንድ ሊግ ላይ ብዙ ሪከርዶች ሊመዘገቡ እንደሚችሉ ሲጠበቅ ሰንብቷል፡፡ በተለይ በ5ሺ ሜትር ሴቶች በውድድር ዘመኑ ሁለት ጊዜ ሪከርድ ለመስበር ሙከራ አድርገው እርስበራስ ሊገናኙ የበቁት ገንዘቤ ዲባባ እና አልማዝ አያና በመሳተፋቸው በሚያደርጉት ፉክክር ክብረወሰን ሊሰበር እንደሚችል ከፍተኛ ግምት ፈጥሯል፡፡ በ5ሺ ሜትር የዓለም ሪከርድ ከሰባት ዓመታት በፊት በኖርዌይ  ኦስሎ ከተማ ላይ በጥሩነሽ ዲባባ 14 ደቂቃዎች ከ11.15 ሰከንዶች በሆነ ጊዜ ተመዝግቦ ቆይቷል፡፡
አልማዝና ገንዘቤ ዘንድሮ በ5ሺ ሜትር ሪከርድ ለማስመዝገብ ከጫፍ የደረሱበት ብቃት ላይ ናቸው፡፡ ሁለቱ አትሌቶች በሩጫ ዘመናቸው ለፈረንሳዩ ዳይመንድ ሊግ ከመገናኘታቸው በፊት በሁሉም ውድድሮች ለ8 ጊዜያት ተገናኝተዋል፡፡ በስድስቱ ገንዘቤ ስታሸንፍ ሁለቴ ያሸነፈችው አልማዝ ነበረች፡፡ ሁለቱ አትሌቶች ባለፈው ዓመት 3 ጊዜ በ5ሺ ሜትር በተገናኙበት ወቅት በሮምና በሞናኮ ከተሞች ገንዘቤ ስታሸንፍ በሞሮኮ ማራካሽ በተከናወነው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ደግሞ የቀደመችው አልማዝ ነበረች፡፡ ዘንድሮ  አልማዝ አያና በሻንጋይ ከተማ በተደረገው የዳይመንድ ሊግ ውድድር 14 ደቂቃዎች ከ14.32 ሰከንዶች በሆነ ጊዜ በማሸነፍ የዓመቱን ፈጣን ሰዓት አስመዝግባለች፡፡ ገንዘቤ ዲባባ በበኩሏ በአሜሪካዋ ከተማ ዩጂን  ከተማ በተደረገው ዳይመንድ ሊግ ላይ በትራክ 5ሺ ሜትር የግሏን ፈጣን ሰዓት አስመዝግባለች፡፡ ክብረወሰኑን ለመስበርም በ10 ሰከንዶች በመዘግይቷ አልተሳካላትም፡፡
የ5ሺ ሜትር ሴቶች የዓለም ሪከርድ ሊሰበር እንደሚችል የተገመተው  በገንዘቤ ዲባባ እና በአልማዝ አያና መገናኘት ብቻ አይደለም፡፡ በሴቶች 5 ሺ ሜትር የዳይመንድ ሊግ ውድድሩ ላይ ተሳታፊ ከሚሆኑት መካከል በ2015 የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ ከአንድ እስከ አራት ደረጃ ያገኙ፤ በውድድር ዘመኑ ፈጣን ሰዓት ያስመዘገቡ ሰባት ምርጥ አትሌቶች መኖራቸውም ነው፡፡ በእርግጥ በርቀቱ የምንግዜም ፈጣን ሰዓት ደረጃ 3ኛ እና 4ኛ ፈጣን ሰዓትን ያስመዘገቡት አልማዝ እና ገንዘቤ ናቸው፡፡ የእነዚህ ተሳታፊ አትሌቶች የተቀራረበ ብቃት ለሪከርዱ መሰበር ምክንያት ሊሆን እንደሚችል እየተገመተ ነው፡፡ አልማዝ አያና የርቀቱን ሪከርድ ለመስበር ካስመዘገበችው ፈጣን ሰዓት 3.18 ሰከንዶችን መቀነስ ሲጠበቅባት ገንዘቤ ለመቀነስ የሚጠበቅባት 7.70 ሰከንዶች ይሆናል፡፡ ጥሩነሽ ዲባባ በ2008 እኤአ ላይ በኖርዌይ ኦስሎ  ከተማ ውስጥ 14፡11 .15 ሪከርድ ስታስመዘግብ አስቀድሞ የነበረውን ክብረወሰን በ5.48 ሰከንዶች አሻሽላ እንዲሁም ይግሏን ፈጣን ሰዓት በ16.27 ሰከንዶች በመቀነሷ ነው፡፡ ይሄው የጥሩነሽ ዲባባ ሪከርድ ከተመዘገበ ዛሬ 7 ዓመታት ከ28 ቀናት ይሆነዋል። ከጥሩነሽ ዲባባ በፊት መሰረት ደፋር በ2006 እኤአ ኒውዮርክ ላይ በ14፡24 .53 ለ1 ዓመት ከ12 ቀናት እንዲሁም በ2007 እኤአ በኖርዌይ ኦስሎ በ14፡16 .63 ለ357 ቀናት ሪከርዱን ይዛ በመቆየት አስቀድሞ ከነበረው ክብረወሰን 8.05 ሰከንዶች ቀንሳ ነበር፡፡
ውድድሩ የሚካሄደው በሴንተዴኒስ በሚገኘው ስታድ ዴ ፍራንስ ሲሆን የአየር ንብረቱ እስከ 94 ዲግሪ ፋራናይት መገመቱ ክብረወሰኑን ለመስበር አዳጋች ያደርገዋል እየተባለ ነው፡፡
ከአልማዝ አያና እና ከገንዘቤ ዲባባ ሌላ የሚሳተፉት  የኢትዮጵያ አትሌቶች ገለቴ ቡርቃ፤ አዝመራ ገብሩ፤ ነፃነት ጉደታ፤ አለሚቱ ሃሮዬና ሰንበሬ ተፈሪ ሲሆኑ ሌሎች 5 የኬንያ፤ የፖላንድ፤ የዩናይትድ አረብኢምሬትስ፤ የፖርቱጋልና የዩክሬን አትሌቶችም ይፎካከራሉ፡፡
6ኛው ዳይመንድ ሊግ በዶሃ ሲጀመር ሶስት የዳይመንድ ሊግ ክብረወሰኖች በ200 ሜትር ሴቶች፤  በሴቶች 100 ሜትር መሰናክል እና በስሉስ ዝላይ የተመዘገቡ ሲሆን ኢትዮጵያዊ አሸናፊ አልነበረም፡፡ በ2ኛው ከተማ ቻይና ሻንጋይ ላይ በ5ሺ ሜትር ሴቶች አልማዝ አያና በድንቅ ብቃት ስታሸንፍ የዓመቱን ምርጥ ሰዓት አስመዝግባ ነው፡፡ በ3ኛው ከተማ በአሜሪካ ዩጂን ላይ ገንዘቤ ዲባባ በተመሳሳይ ርቀት ብታሸንፍም የአልማዝ አያናን ፈጣን ሰዓት እና የርቀቱን ሪከርድ ለማስመዝገብ የነበራት እቅድ አልተሳካም፡፡ በ4ኛዋ ከተማ ጣሊያን ሮም ላይ ሶስተኛውና አራተኛው የኢትዮጵያውያን የዳይመንድ ሊጎች ተመዝግበዋል፡፡ በ1500 ሜትር ባሸነፈው መሃመድ አማንና በ5ሺ ሜትር የመጀመርያ የዳይመንድ ድሉን ባገኘው የ17 አመቱ ዮሚፍ ቀጀልቻ የተመዘገቡት ናቸው፡፡ በ5ኛዋ ከተማ በእንግሊዝ በርሚንግሃም ያሸነፈ ኢትዮጵያዊ አልነበረም፡፡ በ6ኛዋ ከተማ በኖርዌይ ኦስሎ ግን ገንዘቤ ዲባባ ሁለተኛው የዳይመንድ ሊግ ድሏን በ5ሺ ሜትር አሸንፋለች፡፡ 6ኛው ዳይመንድ ሊግ በ7ኛዋ ከተማ በአሜሪካ ኒውዮርክ ሲቀጥል ኢትዮጵያዊ አሸናፊ አልነበረም፡፡
ከፈረንሳይ ከተማ ፓሪስ በፊት 6ኛው ዳይመንድ ሊግ በኳታር ዶሃ፤ በቻይና ሻንጋይ፤ በአሜሪካ ዩጂን፤ በጣሊያን ሮም፤ በእንግሊዝ በርሚንግሃም፤ በኖርዌይ ኦስሎ፤ 6 የዳይመንድ ሊግ ዙሮች ተካሂዷል፡፡ 6ኛው ዳይመንድ ሊጉ በሰባተኛው ከተማ ፈረንሳይ ሴንቲዴኒስ  ዛሬ ከተካሄደ በኋላ ቀሪዎቹ ከተሞች የስዊዘርላን ሉዛኔ፤ በሞናኮ ፎንትቪሌ፤ በእንግሊዝ ለንደን፤ በስዊድን ስቶክ ሆልም፤ በስዊዘርላንድ ዙሪክ እንዲሁም የውድድር ዘመኑ ፍፃሜ በቤልጅዬም ብራሰልስ የሚደረግ ይሆናል፡፡
ባለፉት 5 የዳይመንድ ሊግ የውድድር ዘመኖች 39 የዳይመንድ ሊግ አሸናፊዎች ያስመዘገበችው አሜሪካ አንደኛ ደረጃ ሲኖራት፤ ኬንያ በ26 ሁለተኛ ደረጃ ላይ ናት፡፡ ጃማይካ በ13 የዳይመንድ ሊግ ድሎች ሶስተኛ ደረጃ ስትይዝ፤ ኢትዮጵያ በ2012 እኤአ ላይ አበባ አረጋዊ በ1500 ሜትር ዜግነቷን ሳትቀይር ያስመዘገበችውን ድል ጨምሮ በ8 የዳይመንድ ሊግ ድሎች አራተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ የኢትዮጵያ ስምንት የዳይመንድ ሊግ ድሎች በአምስት አትሌቶች የተመዘገቡ ናቸው፡፡ በ800 ሜትር መሃመድ አማን በ2012 እና በ2013 እኤአ አሸንፏል። በ5ሺ ሜትር ወንዶች ካላፉት አምስት የዳይመንድ ሊግ የውድድር ዘመኖች  አራቱን ሁለት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሸንፈዋል፡፡ በ2010 እና 2011 እኤአ ኢማና መርጋ እንዲሁም በ2013 እኤአ የኔው ያለው ናቸው፡፡ አበባ አረጋዊ ዜግነቷን ሳትለውጥ በፊት በ1500 ሜትር በ2012 እኤአ ላይ አሸናፊ ነበረች፡፡ በሴቶች 5ሺ ሜትር መሰረት ደፋር በ2013 እኤአ ያሸነፈች ሲሆን በ3ሺ ሜትር መሰናክል ደግሞ 2014 እኤአ ላይ ህይወት አያሌው ድል አድርጋለች፡፡ ባለፉት አምስት የዳይመንድ ሊግ የውድድር ዘመኖች ኢትዮጵያውያን በአምስት የውድድር መደቦች አምስት የዳይመንድ ሊግ ክብረወሰኖችን አስመዝግበዋል። እነሱም በ2011 እኤአ የኔው አላምረው በ3ሺ ሜትር፤ በ2012 ደጀነ ገብረመስቀል በ5ሺ ሜትር ፤ በ2011 በቀነኒሳ በቀለ በ10ሺ ፤ በ2012 እኤአ በጥሩነሽ ዲባባ በ10ሺ ሜትር እንዲሁም በ2015 በአልማዝ አያነ በ5ሺ ሜትር የተመዘገቡት ናቸው፡፡በሁለቱም ፆታዎች በ16 የውድድር መደቦች የዳይመንድ ሊጉ ፉክክር የሚካሄድ ሲሆን ከ14 ከሞች እያንዳንዱ የውድድር መደብ ሰባት ጊዜ ይካሄዳል። በየከተማው በሚካሄድ የዳይመንድ ሊግ ፉክክሩ አሸናፊውቅ 10 ሺ ዶላር ይሸለማል፡፡ በየውድድር መደቡ ከፍተኛውን ነጥብ ይዞ የሚያጠናቅቅ አትሌት በሊጉ ማጠቃለያ የ40 ሺ ዶላር እና የዳይመንድ ሊግ ዋንጫ ተሸላሚ ይሆናል፡፡

   በ2016 እኤአ ሩዋንዳ ወደ የምታዘጋጀው አራተኛው የቻን ውድድር ለማለፍ የሚደረገው የመጀመርያ ዙር ማጣሪያ  በመልስ ጨዋታዎች ይቀጥላል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከኬኒያ አቻው ጋር  በመልስ ጨዋታው በናይሮቢው ናያዮ ስታድዬም ይፋለማል፡፡  ለ1 ሳምንት ያህል በሃዋሳ ከተማ ዝግጅት ያደረገው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን 24 ተጫዋቾችን በመያዝ ወደ ኬኒያ ያቀናው ባለፈው ረቡዕ ነበር፡፡ ዋና አስልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ቡድናቸው ውጤቱን እንደሚያስጠብቅ ተማምነዋል፡፡ ወደ የመጨረሻው የማጣርያ ምእራፍ ለማለፍ ከሜዳው ውጭ በሚያደርገው የመልስ ትንቅንቅ አጥቅቶ እንደሚጫወት ተናግረዋል፡፡
ከሁለት ሳምንት በፊት የመጀመሪያው የማጣሪያ ጨዋታ በባህርዳር ሲደረግ በአስቻለው ግርማ እና በጋቶም ፓኖም ጎሎች 2ለ0 በሆነ ውጤት ያሸነፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን  ነበር፡፡ በመልስ ጨዋታው ዋልያዎቹ ከማጣርያው ሊሰናበቱ የሚችሉት ከሜዳቸው ውጭ በሶስት ንፁህ ጎሎች ልዩነት ከተሸነፉ ብቻ ነው።  በየትኛውም ቅድመ ትንበያ ኬንያን ጥሎ ለማለፍ ሰፊ እድል የሚኖረው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ሲሆን በምስራቅ አፍሪካ ዞን ሩዋንዳ ላይ ለሚካሄደው የቻን ውድድር ማለፍ ዘርፈ ብዙ መነቃቃቶችን ሊፈጥር ይችላል፡፡ የኢትዮጵያና የኬንያ አሸናፊ በመጨረሻው ዙር  ማጣርያ ሊገናኝ የሚችለው ከብሩንዲ እና ጅቡቲ አሸናፊ ጋር ነው፡፡ ሁለቱ ቡድኖች በመጀመርያ ጨዋታቸው ብሩንዲ ከሜዳዋ ውጭ 2ለ1 ጅቡቲን አሸንፋለች፡፡ ዋልያዎቹ በምስራቅ አፍሪካ ጠንካራ ሊባል የሚችለውን የኬንያ ብሄራዊ ቡድን ጥለው ማለፍ ከቻሉ ጅቡቲንም ሆነ ብሩንዲን በደርሶ መልስ ለማሸነፍ የሚቸገሩ አይመስልም።  የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በታሪክ ለሁለተኛ ጊዜ በቻን ውድድር የመሳተፍ እድሉንም የሚያጠናክረው ኬንያን ጥሎ ማለፍ ሲችል ነው፡፡
ኢንስትራክተር ዮሃንስ ሳህሌ ወደ ኬንያ ለመልሱ ጨዋታ ከማቅናታቸው በፊት የቡድናቸውን ወቅታዊ ብቃት ሲገልፁ፤ የቡድኑ መንፈስ ከፍ ያለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ መጠነኛ ጉዳት ላይ የነበረው ሳላዲን ባርጌቾም ሙሉ በሙሉ ጤነኛ በመሆኑ ልምምድ መስራቱን አሳውቀዋል።
ለመልሱ ጨዋታ ወደ ናይሮቢ ያቀናው የዋልያዎቹ አባላት ስም ዝርዝር ይፋ ከሆነ በኋላ ለመረዳት የተቻለው ብሔራዊ ቡድኑ በአዳዲስ ተጨዋቾች በመገንባት እየሰፋ መሄዱን ነው፡፡
ግብ ጠባቂዎች ታሪክ ጌትነት ፣ አቤል ማሞና ቴዎድሮስ ጌትነት ፤ ተከላካዮች ዘካሪያስ ቱጂ  ፣ አስቻለው ታመነ ፣  ስዩም ተስፋዬ  ፣ ሳላሃዲን ባርጌቾ  ፣ ተካልኝ ደጀኔ ፣ ግርማ በቀለ ፣  በረከት ቦጋለ ፣  ሞገስ ታደሰና  ሙጂብ ቃሲም ፤ አማካዮች  ጋቶች ፓኖም ፣  ምንተስኖት አዳነ ፣ ፍሬው ሰለሞን ፣ በሀይሉ አሰፋ፣  ብሩክ ቃልቦሬ፣  ኤፍሬም አሻሞና አስቻለው ግርማ ፤ አጥቂዎች ቢኒያም አሰፋ ፣ ራምኬል ሎክ፣  ዮናታን ከበደ ፣ ኤፍሬም ቀሬ እና ባዬ ገዛሀኝ  ናቸው፡፡  
ይህ በእንዲህ እንዳለ በባህር ዳር የደረሰባቸውን የመጀመርያ ጨዋታ ሽንፈት ለመቀልበስ ኬንያውያን በሁሉም አቅጣጫዎች  ሲዘጋጁ ነበር፡፡ ኬንያ ለቻን ያዘጋጀችው ቡድን ሰሞኑን እንኳን ሁለት ጨዋታዎችን ከአገሪቱ ትልቅ ክለብ ጎሮማሃያ ጋር አድርገዋል፡፡ በመጀመርያው ጨዋታ 1ለ1 አቻ ተለያይተው በሁለተኛው ጨዋታ 1ለ0 አሸንፈዋል፡፡ በሜዳችን ውጤት ይዘን ለመውጣት ከፍተኛ ጥረት አድርገን ወደ ቀጣዩ ዙር እናልፋለን በማለት በልበሙሉነት ተናግረው የኬኒያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ቦቢ ዊልያምሰን ቡድናቸውን ለማነቃቃት ሞክረዋል፡፡ ከመልሱ ጨዋታ በፊት የኬንያ ብሄራዊ ቡድን ስታር ታይምስ በተባለ የብሮድካስት ኩባንያ ለሚቀጥሉት አምስት አመታት በ110 ሚሊዮን ብር ስፖንሰርሺፕ አግኝቷል፡፡ ስታር ታይምስ የሃራምቤ ኮከቦች የአፍሪካ ዋንጫ እና የቻን ማጣርያ ጨዋታዎችን ቀጥታ ስርጭት ለማከናወን ተዋውሏል። የመጀመርያውን ስርጭት ዛሬ ኢትዮጵያ እና ኬንያ በናያዮ ስታድዬም በሚያደርጉት ጨዋታ ይጀምራል፡፡

ኢትዮጵያ በ2015 መካሄድ ያለበትን 38ኛው ሴካፋ ሲኒዬር ቻሌንጅ ካፕን እንደምታስተናግድ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አስታወቀ፡፡  ፕሬዝደንቱ ጁነዲ ባሻ በግል የትዊተር ገፃቸው ባሰፈሩት ማስታወሻ ፌደሬሽኑ የሴካፋ ዋንጫን በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የክልል ከተሞች ለማዘጋጀት ማቀዱን አመልክተዋል። ለብሄራዊቡድኑ የአፍሪካ እና የቻን ማጣርያዎች ምቹ የሆነው ባህርዳር ስታድዬም ለሴካፋ ውድድር ማስተናገጃነት ቅድሚያ ከሚያገኙት ስታድዬሞች አንዱ መሆኑ በመነገር ላይ ነው፡፡ የ38ኛው ሴካፋ ሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕ መስተንግዶ ከተሳካ  ኢትዮጵያ ለአራተኛ ግዜ ማዘጋጀቷ ይሆናል፡፡  በ1987 እኤአ ፣ በ2004 እና በ2006 እኤአ ኢትዮጵያ የሴካፋ ዋንጫን በተሳካ ሁኔታ እንዳዘጋጀች ይታወቃል፡፡ በሌላ በኩል የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት በ2020 እኤአ 5ኛውን የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ (ቻን) ውድድር ለማዘጋጀት እድል እንዳላትም ገልፀዋል፡፡ ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት መካሄድ የነበረበትን የ2014 ሴካፋ ሲኒዬር ቻሌንጅ ካፕ ለማዘጋጀት ተመርጣ የነበረ ቢሆንም ከኢቦላ ወረረሽኝ፤ በአገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ውድድሮች መደራራብ እና በሌሎች ተያያዥ ችግሮች መስተንግዶውን እንደተወች የሚታወስ ነበር፡፡ የዘንድሮውን ሻምፒዮና ደግሞ ሩዋንዳ ለማዘጋጀት ከተመረጠች በኋላ በ2016 እኤአ ከምታካሂደው 4ኛው የቻን ውድድር ጋር በተያያዘ መስተንግዶውን ለማከናወን ያዳግተኛል በማለቷ ኢትዮጵያ በምትክነት ውድድሩን ለማስተናገድ እንደወሰነላት ታውቋል፡፡ ሴካፋ ሲነዬርስ ቻሌንጅ ካፕ ባለፈው የውድድር ዘመን ኢትዮጵያ ከመስተንግዶ ራሷን በማግለሏ ሳይካሄድ የቀረ ሲሆን ከሁለት ዓመት በፊት ሻምፒዮናው ለ37ኛ ጊዜ በኬንያ አስተናጋጅነት በተካሄደበት ወቅት ኬንያ 2ለ0 በሆነ ውጤት ሱዳንን በማሸነፍ ሻምፒዮን ሆናለች፡፡
የሴካፋ ምክር ቤት 12 አባል አገራት ያሉት ሲሆን እነሱም ብሩንዲ፤ ጅቡቲ፤ ኤርትራ፤ ኢትዮጵያ፤ ኬንያ፤ ሩዋንዳ፤ ሶማሊያ፤ ደቡብ ሱዳን፤ሱዳን፤ ታንዛኒያ ኡጋንዳ እና ዛንዚባር ናቸው፡፡  ምክር ቤቱ በየውድድር ዘመኑ 5 ውድድሮች የሚያካሂድ ሲሆን እነሱም ሴካፋ ሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕ፤ ሴካፋ ካጋሜ ካፕ፤ ሴካፋ ናይልቤዚን ካፕ፤ እንዲሁም የሴካፋ ሀ17 እና ሀ 20 ውድድሮችን ናቸው፡፡
በሴካፋ ሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕ የወቅቱ ሻምፒዮን በ2013 እኤአ ላይ ያዘጋጀችውን ዋንጫ ያሸነፈችው እና በአጠቃላይ 6 ጊዜ ያሸነፈችው ኬንያ ናት፡፡ ኡጋንዳ ለ13 ጊዜያት የዞኑ ሻምፒዮን በመሆን ከፍተኛውን ውጤት ይዛለች፡፡ ኢትዮጵያ በ18 ሴካፋ ሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕ  የተሳትፎ ታሪኳ 4 ጊዜ ሻምፒዮን፤ 1 ጊዜ 3ኛ ደረጃ እንዲሁም 2 ጊዜ አራተኛ ደረጃ በማግኘት ከኡጋንዳ እና ኬንያ በመቀጠል በክፈተኛ ውጤት ሶስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡

ከ2 ሳምንት በኋላ በታንዛኒያ ዋና ከተማ ዳሬሰላም መካሄድ በሚጀምረው 40 የምስራቅ አፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮና (ካጋሜ ካፕ) ላይ ኢትዮጵያን በመወከል አዳማ ከነማ ሊሳተፍ ነው፡፡  ዘንድሮ በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ላይ በጥሩ ተፎካካሪነት ሶስተኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀው አዳማ ከነማ በካጋሜ ካፕ ሲሳተፍ በተከታታይ የውድድር ዘመናት ለሁለተኛ ጊዜው ነው፡፡ በዞኑ የክለቦች ሻምፒዮና ላይ የፕሪሚዬር ሊጉ ሻምፒዮን  ቅዱስ ጊዮርጊስ በቀጥታ ተሳታፊ ነበረ፡፡  ካልተሳተፈ ደግሞ በሁለተኛ ደረጃ የጨረሰው ደደቢት መተካት ይችላል፡፡ ይሁንና ሁለቱም ክለቦች ሰሞኑን በተጨዋቾች የዝውውር ህገ ደንብ የተፈከፌደሬሽኑ ጋር በፈጠሩት ሙግት፤ ተሳትፏቸውን ሰርዘዋል ተብሏል፡፡ አዳማ ከነማ በፕሪሚዬር ሊጉ ባገኘው ሶስተኛው ደረጃ የካጋሜ ካፕ ተሳትፎው በፌደሬሽን በኩል ተረጋግጦለታል፡፡  
የሴካፋ ምክርቤት በታንዛኒያ ዋና ከተማ ዳሬሰላም በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ባካሄደው ስነስርዓት ላይ ለ40ኛው የካጋሜ ካፕ የምድብ ድልድሉን አውጥቷል። ተሳታፊዎቹ 13  ክለቦች በ3 ምድቦች ተደልድለዋል። በምድብ 1 የአምስት ጊዜያት ሻምፒዮኑ የታንዛኒያው ክለብ ያንጋ፤ ከኬንያው ታላቅ ክለብ ጎሮማሃያ፤ ከሱዳኑ አል ካርቱም፤ ከሶማሊያው ቴሌኮም እና ከዛንዚባሩ ኬኤምኬኤም ፤ በምድብ 2 የሩዋንዳው ኤፒአር፤ የሱዳኑ አልሃሊ ሸንዲ፤ የብሩንዲው ኤልኤልቢ እና የሱማሊያው ኤልማን እንዲሁም በምድብ 3 የታንዛኒያው አዛም፤ የደቡብ ሱዳኑ ማልካያ፤ የኡጋንዳው ካምፓላ ሲቲ እና የኢትዮጵያው አዳማ ከነማ ተደልድለዋል፡፡ የአምናው ሻምፒዮን የነበረው የሱዳኑ ክለብ ኤልሜሪክ በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ላይ ባደረገው ትኩረት ተሳትፎውን በመተው አልካርቱም ተክቶት ገብቷል፡፡ በ2014 እኤአ ላይ ውድድሩ በሩዋንዳ አስተናጋጅነት በተካሄደበት ወቅት የሱዳኑ ክለብ ኤል ሜሪክ የሩዋንዳውን ኤፒአር 1ለ0 አሸንፎ ሻምፒዮን እንደሆነ ይታወሳል፡፡ ከ3ቱ ምድቦች አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ የሚያገኙት እና ሁለት በምርጥ ሶስትኛ ደረጃ የሚጨርሱት ክለቦች ወደሩብ ፍፃሜ ያልፋሉ፡፡ በካጋሜ ካፕ ለሚያሸንፈው ክለብ 30ሺ ዶላር ሽልማት ሲበረከት፤ ለሁለተኛ 20ሺ ዶላር እንዲሁም ለሶስተኛ ደረጃ 10ሺ ዶላር ይሸለማል። የካጋሜ ካፕ 60ሺ ተመልካች በሚይዘው የዳሬሰላሙ ብሄራዊ ስታድዬም ለ3 ሳምንት የሚካሄድ ሲሆን፤ ሁሉም ግጥሚያዎች በሱፕርስፖርት ዎርልድሻምፒዮንስ ቻናል 219 ላይ ይተላለፋሉ፡፡
በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ እየተመራ በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ሶስተኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀው አዳማ ከነማ በካሜ ካፕ ሲሳተፍ ለሁለተኛ ጊዜ ይሆናል። ባለፈው የውድድር ዘመን 39ኛው የካጋሜ ካፕ ውድድር በሩዋንዳ አስተናጋጅነት በተካሄደበት ወቅት አዳማ ከነማ ነበረበት፡፡ በምድብ 1 ከታንዛኒያው አዛም፤ ከደቡብ ሱዳኑ አተልባራ ከሩዋንዳው ራዮን ስፖርትስ እና ከዛንዚባሩ ኬኤምኬኤም ጋር ተደልድሎ 4 ጨዋታዎችን አድርጓል፡፡ በመጀመርያው ጨዋታው በሩዋንዳው ራዮን ስፖርትስ 2ለ1 ከተሸነፈ በኋላ በሁለተኛው ጨዋታ ከዛንዚባሩ ኬኤምኬኤም ጋር 1ለ1 እንዲሁም በሶስተኛው ጨዋታ ከደቡብ ሱዳኑ አተልባራ 1ለ1 አቻ ቢለያይም በመጨረሻው የምድቡ ጨዋታ በታንዛኒያው አዛም 4ለ1 ተሸንፏል፡፡ ስለሆነም በ4 ጨዋታዎች ሁለት ነጥብ አስመዝግቦ በ4 የግብ እዳ በምድቡ ሶስተኛ ደረጃ ይዞ በማጠናቀቅ ከውድድሩ መሰናበቱ ይታወሳል፡፡ በአራቱም ጨዋታዎች አዳማ ከነማ በተጋጣሚዎቹ ላይ ጎሎችን ያስመዘገበ ሲሆን ሁለት ጎሎችን ሞሸንዲ የተባለ ተጨዋች በራዮን ስፖርትስ እና በኬኤምኬኤም ላይ እንዲሁም እያንዳንዳቸው አንድአንድ ጎሎችን ኢብሳ አትልባራ ላይ ደባስ ደግሞ በአዛም ላይ አስመዝግበው ነበር፡፡
በምስራቅ አፍሪካ የክለቦች ሻምፒዮና ታሪክ ኢትዮጵያን የወከለ ክለብ ዋንጫውን አሸንፎ የማያውቅ ሲሆን ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገበው በ2010 እኤአ ላይ ለዋንጫ የደረሰው ቅዱስ ጊዮርጊስ ብቻ  ነው፡፡ ካጋሜ ካፕ በ1974 እኤአ የተጀመረ ሲሆን የታንዛኒያናው ክለብ ሲምባ ለስድስት ጊዜያት ሻምፒዮን በመሆን ከፍተኛውን ውጤት አስመዝግቧል፡፡ በአገር  ደረጃ የኬንያ ክለቦች 15 ጊዜ፤ የታንዛኒያ ክለቦች 11 ጊዜ፤ የኡጋንዳ ክለቦች 5 ጊዜ የሩዋንዳ ክለቦች 4 ጊዜ፤ የሱዳን ክለቦች 3 ጊዜ እንዲሁም የብሩንዲ ክለብ 1 ጊዜ ማሸነፍ ችለዋል፡፡


በወጣቷ ገጣሚ ፅጌረዳ ጌታቸው የተፃፉ የእንግሊዝኛ ግጥሞች የየዘ “The Unspoken Outlook” የተሰኘ የግጥም መድበል በዛሬው ዕለት ከ10፡30 ጀምሮ ቦሌ ኤርፖርት መዳረሻ ጋ በሚገኘው ቲኬ ህንፃ፣ 8ኛ ፎቅ ላይ ይመረቃል፡፡ በምረቃው ሥነ -ሥርዓት ላይ የስነ ፅሁፍ ባለሙያ ሂሳዊ ዳሰሳ ያቀርባሉ ተብሏል፡፡
በ84 ገፆች የተቀነበበው የግጥም መድበሉ፤ በ38 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡ ገጣሚዋ ዘንድሮ በሲቪል ኢንጂነሪንግ ከአምስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ እንደምትመረቅ ታውቋል፡፡