ዛሬ፤ የረመዳን ፆምን ፍፃሜ ምክንያት በማድረግ፤  እድሪስ ሻህ በተባለው ዝነኛ ሱፊ አንድ መፅሐፍ ላይ ያተኮረ ጨዋታ ይዤላችሁ መጥቻለሁ፡፡ እድሪስ ሻህ፤ ‹‹የመፅሐፉ መፅሐፍ›› የሚል ትልቅ ማዕረግ በሰጠው እና ዘጠኝ ገፆች ብቻ ባሉት መፅሐፍ የሰፈሩ ታሪኮችን ነው - (በእያንዳንዱ ገፅ የሰፈረው ፅሑፍም ከግማሽ ገፅ እንደሚያንስ ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡) እድሪስ ሻህ፤ ሁለት መስመሮች ባሉት መቅድም ኤዞፕን ጠቅሶ ይጀምራል፡፡
ኤዞፕም በአንዱ ተረቱ እንዲህ ይላል፤
‹‹አንድ ጊዜ፤ የተወሰኑ የዱር አራዊቶች ተሰብስበው፤ ከአንዲት ሴት አንበሳ ዘንድ ሄዱ። እናም እንዲህ ሲሉ ጠየቋት፤ ‹‹ለመሆኑ አንዲት ሴት አንበሳ በአንድ ጊዜ ምን ያህል ግልገሎችን ትወልዳለች?›› በማለት ጠየቋት። እርሷም፤ ‹‹በአንድ ጊዜ የምትወልደው አንድ ነው፡፡ ግን ያ አንድ፤ አንበሳ ነው›› አለቻቸው፡፡
ከፍ ሲል የጠቀስኩት ተረት፤ ደራሲው ‹‹The Book of the Book›› የሚል ርዕስ በሰጠው እና የባለ ዘጠኝ ገፅ መፅሐፍ መቅድም የሰፈረ ሲሆን፤ ከመቅድሙ ቀደም ብሎ ከመፅሐፉ የሽፋን ገፅ ሌላ የተጠቀሰ ቃል አለ፡፡ ‹‹The Book of the Book›› ከሚለው የመፅሐፉ ርዕስ ሥር፤ ‹‹The value of the dwelling is in the dweller›› የሚል ጥንታዊ ብሂል ሰፍሯል፡፡ ሲተረጎም፤ ‹‹የመኖሪያ ጎጆው ዋጋ በነዋሪው ውስጥ ይገኛል›› የሚል ይሆናል። ነገሩ በዚሁ ጎዳና ከታየ፤ እድሪስ ሻህ ‹‹በዚህ መፅሐፍ ያቀረብኩላችሁ ተረቶች ዋጋ የሚገኘው፤ በተደራሲው ውስጥ ነው›› ማለቱ መሰለኝ፡፡
ደግሞም ከፍ ሲል እንደ ገለፅኩት፤ የኤዞፕን ተረት ጠቅሷል፡፡ እድሪስ ሻህ፤ የኤዞፕን ተረት በመቅድሙ ሲጠቅስ ለማስተላለፍ የፈለገው መልዕክት ግልፅ ይመስለኛል፡፡ መልዕክቱ በሥነ ግጥም መልክ ቢነገር፤ ‹‹አስር ቢወለድ አስር ነው ጉዱ፤ ጀግና ከሆነ ይባቃል አንዱ›› ሊባል እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ በሱፊ ቅኔ እና ቁጥብነት የሚሄድ በመሆኑ፤ ሻህ ያለ ሐተታ ይናገራል። ቅኔው ቢፈታ፤ ‹‹የቀረቡት ተረቶች የሴት አንበሳ ዓይነት ተፈጥሮ አላቸው›› የሚል ሐሳብ የሚገኝ ይመስለኛል። በአውዱ ተደንግጎ የታወጀው ሐሳብ፤ ‹‹ከዚህ በታች፤ የምታነቧቸው ‹ተረቶች› ብዙ ሐሳብ አይፈለፍሉም። በአንድ ጊዜ የሚወልዱት አንድ ልጅ ነው፡፡ ግን የሚወልዱት ያ አንድ ልጅ፤ አንበሳ ነው›› የሚል ነው፡፡ እኔ በመደነቅ አነበብኳቸው፡፡ እናንተም አሁን አንብቧቸው፡፡
በቅድሚያ አንድ ማሳሰቢያ አለኝ፡፡ ተረቶቹ፤ የተባ አዕምሮ ባላቸው የየትውልዱ የሱፊ መምህራን በደንብ እየተሳሉ ከዘመን ዘመን እየተሸጋገሩ የመጡ በመሆናቸው፤ ተፈላጊውን መልዕክት እንዳላዛንፍ በመስጋት፤ ለእኛ አንባቢያንን እንዲመቹ ለማድረግ በማሰብ ብዙ ከመነካካት ተቆጥቢያለሁ፡፡ እንግዲህ እነሆ፤
ተረት ሲነገር የተለመደ ወግ በመሆኑ፤ ‹‹ተረት - ተረት›› ብያለሁ፡፡ ግን ምላሻችሁን ትንሽ ቀየር ማድረግ ይኖርባችኋል፤ ‹‹የእውነት በረት›› በሉኝ፡፡
ድሮ - ድሮ፤ እውነትን የተረዳ አንድ ደርቡሽ ነበረ። ይህ ደርቡሽ፤ እኔ የማውቀውን ነገር ለሰዎች ከመናገሬ በፊት፤ በዚህ በተራው ዓለም የኑሮ ስርዓት ገብቼ፤ ባለሥልጣን መሆን አለብኝ ሲል ወሰነ፡፡ ስለዚህ ይህን ውሳኔውን እውን ለማድረግ በማሰብ፤ ጠቅላላ ትኩረቱን በግልፅ የሚታይ ሥልጣንን በማግኘት ሥራ ላይ አደረገ፡፡ በጊዜ ሂደት፤ ያ ደርቡሽ ንጉስ ለመሆን ቻለ፡፡
ይህ ደርቡሽ፤ በንጉስነት ጥቂት ጊዜ ካሳለፈ በኋላ፤ ህዝቡ የማስተማር ዘዴውን እንዳልፈለገው ወይም እንዳልወደደው ተገነዘበ፡፡ በእርግጥ ሲያተምር፤ ህዝቡ ትምህርቱን ከልብ የሚከታተል ይመስል ነበር። ሆኖም፤ ሁሉም በማስመሰል አድራጎት ውስጥ ነበሩ፡፡ ማስመሰል ውስጥ የገቡትም ከንጉሱ ሽልማት ማግኘትን ተስፋ አድርገው ወይም ቅጣትን ፈርተው ነበር፡፡ ይህ ንጉስ-ደርቡሽ፤  የሚያውቀውን ነገር ለማስተማር የሚያስችል ጥሩ መሣሪያ  ወይም ዘዬ አልነበረውም፡፡ ሊሞት ትንሽ ቀናት እስኪቀሩት ድረስ ጥሩ የማስተማሪያ ሥልት ማግኘቱ ሳይከሰትለት ቆየ፡፡
አረንጓዴ ለባሹ እንግዳ
አንድ ቀን፤ ሽምግልና እየተጫጫነው የመጣ አንድ ንጉስ ለአደን ወጥቶ ድካም ቢሰማው፤ ዕረፍት ለማድረግ ከአንድ ስፍራ በመቀመጥ ላይ ሳለ፤ ለሐገሩ ባዳ የሆነ እና አረንጓዴ ልብስ የለበሰ አንድ እንግዳ ሰው ወደ እርሱ ያመራ ነበር፡፡ ንጉሡን እጅ ከነሳ በኋላ፤ አንድ ታሪክ ያወራለት ጀመረ፡፡ ይህም ታሪክ፤ አሁን ማውራት የጀመርነው ታሪክ ሲሆን፤ ርዕሱም ‹‹የመፅሐፉ ተረት›› የሚል ነው፡፡ ቀጥሎ የሚመጣው ታሪክ ‹‹የመፅሐፉ ተረት›› የተሰኘው መፅሐፍ የመጀመሪያ ክፍል ነው፡፡
ከተጠበቀው ተቃራኒ
‹በዘመኑ ተወዳዳሪ ያልነበረው አንድ ጠቢብ ሰው ተዝቆ የማያልቅ ከሚመስለው የጥበብ መዝገቡ እየወሰደ ደቀመዛሙርቱን ያስተምር ነበረ፡፡ የዚህ ጠቢብ ተዝቆ የማያልቅ ጥበብ ምንጩ፤ በመኖሪያ ክፍሉ የክብር ቦታ ይዞ የተቀመጠ አንድ ዳጎስ ያለ  ቅፅ ያለው መፅሐፍ መሆኑን ይናገር ነበር፡፡ ይህ ሊቅ ያንን ትልቅ ቅርጽ ያለውን መጽሐፍ ማንም ሰው ገልጦ እንዲያይ አይፈቅድም ነበር፡፡ ኖረ ኖረና ሞተ፡፡ በሞተ ጊዜም በዙሪያው የነበሩ ሰዎች ራሳቸውን የጥበቡ ወራሽ አድርገው በማሰብ፤ እንዲሁም በዛ ዳጎስ ያለ መፅሐፍ ውስጥ የሰፈረውን ዕውቀት የራሳቸው ለማድረግ ጓጉተው፤ መፅሐፉን ገልጦ ለማየት ተሸቀዳደሙ፡፡ ሆኖም ያን ዳጎስ ያለ መፅሐፍ ቢገልጡት፤ ፅሑፍ የሚባል ነገር ያለው በአንድ ገፅ ላይ ብቻ መሆኑን አይተው ተገረሙ፡፡ ግራ ተጋቡ፡፡ ተበሳጩ፡፡ ይባስ ብሎ፤ ለዓይን ማረፊያ የሆኑላቸውን ጥቂት ሐረጎች ለመረዳት ቢሞክሩ የረባ ነገር በማጣታቸው፤ ከቀድሞው በበለጠ እጅጉን ግራ ተጋብተው በንዴት ቱግ አሉ፡፡ ያቺ የዓይን ማረፊያ የሆነች አንድ ዐረፍተ ነገርም፤ ‹‹በመያዣው እና በይዘቱ መካከል ያለውን ልዩነት በተረዳችሁ ጊዜ፤ የዕውቀት ባለቤት ትሆናላችሁ›› የምትል ነበረች፡፡
 የጠቢባኑ አስተያየት
በዘመኑ እጅግ ታዋቂ የሆነ አንድ ትልቅ ጠቢብ ተተኪ ደቀመዛሙርት የሆኑ ተማሪዎች፤ ከመምህራቸው የወረሱትን አንድ መፅሐፍ በመያዝ ወደ ሊቃውንት በመሄዱና ‹‹ይሄ መፅሐፍ አለን። መፅሐፉ እከሌ የተባሉ፤ በዘመናቸው ድንቅ የነበሩ ጠቢብ መፅሀፍ ነው፡፡  አሁን አርፈዋል፡፡ እርሳቸው እንደ ቅርስ ትተውልን የሄዱትም ይህንኑ መፅሐፍ ነው። ሆኖም በዚህ መፅሐፍ ያለውን ምስጢር መርምረን ልናገኘው አልቻልንም፡፡ እናም፤ መፅሐፉን በአንድምታ እንድትፈቱልን እንፈልጋለን›› በማለት መፅሐፉን ሰጧቸው፡፡ እነዚያም ሊቃውንት፤ እልፍ አዕላፍ ህዝብ ያከብራቸው የነበሩ ጠቢብ ሰው ስም የሰፈረበት፤ እንደዚያ ያለ ባለትልቅ ቅጽ መፅሀፍ በማየታቸው እጅግ ተደስተው፤ ‹‹አምጡት፡፡ በርግጥም መርምረን ትክክለኛውን አንድምታ እነግራችኋለን›› በማለት መፅሐፉን ተቀበሏቸው፡፡ ነገር ግን፤ በርካታ ገፆች ያሉት ያ መፅሐፍ ገፆቹ ባዶ ነበሩ፡፡ የተፃፈ ነገር የሚታየው በአንድ ገፅ ላይ ብቻ ነበር፡፡ ተጽፈው የተገኙት ጥቂት ቃላትም ምንም ትርጉም ሊሰጧቸው አልቻሉም፡፡
በመጀመሪያ፤ መፅሐፉን ባመጡት ተማሪዎች ቀለዱባቸው፡፡ ከዚያም ጮሁባቸው፡፡ ጮኸውም፤ በቁጣ ከዚያ አካባቢ አባረሯቸው፡፡ ሊቃውንቱ፤ ተማሪዎቹ መጃጃላቸውን አመኑ፡፡ ያ ዘመን ሊቃውንቱ አዙሮ ለማየት የተቸገሩበት እና በተሰነከለ ህሊና የተጠፈሩበት ዘመን ነበር፡፡ ሊቃውንቱ፤ አንድ ነገር የሚል  መፅሐፍ እንጂ፤ አንድ ነገር የሚያደርግ መፅሐፍ ይኖራል ብለው ጨርሶ ለማሰብ የሚችሉ አልነበሩም፡፡
የደርቡሹ አንድምታ
ተስፋ ያጡ ተማሪዎች መንገድ ሄደው ቢደክማቸው፤ በቃ እንረፍ ብለው የቅፍለት ተጓዦች ማረፊያ ወደሆነ አንድ ሆቴል ጎራ ቢሉ፤ በዚያ አንድ ደርቡሽ አገኙ። ለደርቡሹም የተጨነቁበት እና የተቸገሩበትን ነገር አዋዩት፡፡ እርሱም እንዲህ አላቸው፤
‹‹ከሊቃውንቱ ምን ተማራችሁ?››
ተጓዦቹ ተማሪዎችም እንዲህ አሉ፤
‹‹ምንም የነገሩን እና ያስተማሩን ነገር የለም፡፡››
ደርቡሹም እንዲህ መለሰላቸው፤
‹‹እንዳላችሁት አይደለም፡፡ በተቃራኒው፤ ሊቃውንቱ ሁሉንም ነገር ነግረዋችኋል፡፡ ያ መፅሐፍ እናንተ ባሰባችሁት ወይም እነርሱ በተረዱት መንገድ ሊታይ እንደማይገባ አመልክተዋችኋል፡፡ ምናልባት እናንተ፤ ሊቃውንቱ ጥልቀት አጥተዋል ብላችሁ አስባችሁ ይሆናል፡፡ ነገር ግን፤ በዚያው ልክ እናንተም ንቁ ስሜት አጥታችኋል፡፡ ሊቃውንቱ፤ ከመፅሐፉ ጋር ተያይዞ በተፈጠረው ሁነት አማካይነት ትምህርት ለማስተላለፍ ሲሞክሩ፤ እናንተ ግን አንቀላፍታችኋል›› አላቸው፡፡
ነገር ግን ተማሪዎቹ፤ የተሰጣቸው ትንታኔ ለአዕምሮ በጣም የፀነነ ምስጢር ሆነባቸው፡፡ ሆኖም፤ በአጋጣሚ ወደ ሆቴሉ ጎራ ብሎ ከፍ ሲል የተገለፀውን ቃለ ምልልስ የሰማ እና በመጽሐፉ የተገለፀውን ዕውቀት የተረዳ አንድ ተጓዥ መንገደኛ፤ ‹‹ኦ! ንጉሱ ደርቡሽ!›› ሲል ጮኸ፡፡
ከዚያም፤ ያ አረንጓዴ ልብስ የለበሰ እንግዳ ሰው ከተቀመጠበት ተነሰ እና ሄደ፡፡  (ይቀጥላል)

Published in ጥበብ

- አወዛጋቢው የአገሪቱ ምርጫ ማክሰኞ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል
- ክልላዊው ፍርድ ቤት ግጭቱን ማጣራት ጀምሯል
       በመጪው ማክሰኞ ይከናወናል ተብሎ ከሚጠበቀው የብሩንዲ ምርጫ ጋር በተያያዘ በአገሪቱ የተቀሰቀሰውን ግጭት መፍታት የሚቻልበትን ሁኔታ ለመፍጠር የአገሪቱ የፖለቲካ ሃይሎች በኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩሪ ሙሴቬኒ አደራዳሪነት ውይይት ሊያደርጉ ነው ሲል አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገበ፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለወራት የዘለቀውን የብሩንዲ ግጭት ለማስቆምና በፖለቲካ ሃይሎች መካከል የተፈጠረውን ችግር በድርድር ለመፍታት ሙከራ ቢያደርግም ሳይሳካለት ቀርቷል ያለው ዘገባው፤ ዩሪ ሙሴቬኒ የአገሪቱን መንግስትና የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮችን ለማደራደር ባለፈው ማክሰኞ ቡጁምቡራ መግባታቸውን ገልጿል፡፡
አምስት የምስራቅ አፍሪካ አገራትን በአባልነት በያዘው የኢስት አፍሪካ ኮሚዩኒቲ ድርድሩን እንዲመሩ ባለፈው ሳምንት የተመረጡት ሙሴቬኒ፣ በመጪው ማክሰኞ ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀውን አወዛጋቢ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሰላማዊ ለማድረግና ተልዕኳቸውን ለማሳካት የቻሉትን ሁሉ ጥረት እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፡፡ ሙሴቬኒ ባለፈው ማክሰኞ ከብሩንዲ ፕሬዚዳንት ፔሪ ንኩሩንዚዛ ጋር በጉዳዩ ዙሪያ መወያየታቸውንም ዘገባው ገልጿል። ክልላዊው የምስራቅ አፍሪካ የፍትህ ፍርድ ቤት በበኩሉ፤ በብሩንዲ የተከሰተውን ግጭት በተመለከተ ከሳምንታት በፊት የቀረበለትን ክስ በታንዛኒያ መዲና አሩሻ ባለፈው ማክሰኞ የምርመራ ሂደት መጀመሩን አስታውቋል፡፡
ፓን አፍሪካን ሎየርስ አሶሴሽንና ኢስት አፍሪካን ሲቪል ሶሳይቲ ፎረም የመሰረቱት ክስ፣ የብሩንዲ የህገመንግስት ፍርድ ቤት ለግጭቱ መንስኤ የሆኑት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ፔሪ ንኩሩንዚዛ በምርጫው መሳተፍ ይችላሉ በሚል ያስተላለፈውን ውሳኔ እንዲሻር የሚጠይቅ ነው ተብሏል፡፡
ፕሬዚዳንት ንኩሩንዚዛ ባለፈው ሚያዚያ ወር ላይ ህገ መንግስቱ ከሚፈቅድላቸው ውጪ ለሶስተኛ ዙር በፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለመወዳደር ማስታወቃቸውን ተከትሎ በአገሪቱ በተቀሰቀሰውና ለወራት በዘለቀው ግጭት ከ77 ሰዎች በላይ ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውንና ከ100ሺህ በላይ ዜጎችም ወደ ጎረቤት አገራት መሰደዳቸውን ዘገባው አስታውሷል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

     ከ10 አመታት በላይ የፕሮስቴት ካንሰር ህክምና ተከታትለዋል
   ደቡብ አፍሪካዊው የኖቤል የሰላም ተሸላሚ ሊቃነ ጳጳስ ዴዝሞን ቱቱ ባለፈው ማክሰኞ ባጋጠማቸው ህመም ኬፕታውን ውስጥ በሚገኝ ሆስፒታል ገብተው ህክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኙ ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ምንነቱ በውል ባልተገለጸ በሽታ ተጠቅተው ሆስፒታል የገቡት የ83 አመቱ ዴዝሞን ቱቱ፤ ከአስር አመታት በላይ የፕሮስቴት ካንሰር ህክምና ሲደረግላቸው እንደቆየ ያስታወሰው ዘገባው፣ ወደ ሆስፒታል ያስገባቸው የሰሞኑ ህመም ግን፣ ከዚህ ጋር የተያያዘ መሆን አለመሆኑ አለመታወቁን ገልጿል፡፡ የዴዝሞን ቱቱ ልጅ ሞህ ቱቱ አባቷ ተገቢውን ህክምና በማግኘት ላይ እንደሆኑና በጥቂት ቀናት ውስጥ አገግመው ከሆስፒታል ይወጣሉ የሚል ተስፋ እንዳላት መናገሯን ዘገባው ጠቁሞ፣ ኢንፌክሽን ከመሆኑ ውጪ የህመማቸውን ምንነት በተመለከተ ዝርዝር መረጃ አለመገኘቱን ጠቁሟል፡፡
ከአስር አመታት በላይ በፕሮስቴት ካንሰር ህክምናቸውን ሲከታተሉ የቆዩት ዴዝሞን ቱቱ፣ ባለፈው ታህሳስ ወር ላይም ወደ ሮም ለመጓዝ ይዘውት ነበረውን እቅድ ህክምናቸውን ለመከታተል ሲሉ መሰረዛቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡
የአፓርታይድ አገዛዝን በጽናት በመቃወም የሚታወቁት ዴዝሞን ቱቱ፤ እ.ኤ.አ በ1984 የኖቤል የሰላም ሽልማትን እንደተቀበሉና ከቀናት በፊትም ከባለቤታቸው ሊያ ጋር የጋብቻቸውን 60ኛ አመት በዓል ማክበራቸውን ዘገባው አስታውሷል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

 ባለፈው ግንቦት በምርጫ አሸንፈው ስልጣን የያዙት አዲሱ የናይጀሪያ ፕሬዚዳንት ሙሃማዱ ቡሃሪ፣ አሸባሪውን ቡድን ቦኮ ሃራም ለመደምሰስ የያዙትን ቀዳሚ እቅዳቸውን በአግባቡ ለማሳካት በሚል የቀድሞ የአገሪቱ የምድር ጦር፣ የባህር ሃይል፣ የአየር ሃይልና የመከላከያ መሪዎችን ከስልጣናቸው ማባረራቸውን ዘ ጋርዲያን ዘገበ፡፡
የቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን ባለፉት ስድስት አመታት በአገሪቱ ሰሜን ምስራቃዊ አካባቢዎች 13ሺህ ያህል ዜጎችን ለህልፈተ ህይወት በዳረገውና 1.5 ሚሊዮን ዜጎችን ባፈናቀለው ቦኮ ሃራም ላይ ተገቢ እርምጃ አልወሰዱም በሚል በስፋት ሲወቀሱ እንደቆዩ ያስታወሰው ዘገባው፣ አዲሱ ፕሬዚዳንት ቡሃሪ የሽብር ቡድኑን ሙሉ ለሙሉ ለመደምሰስ እንደሚሰሩ ቃል መግባታቸውንና የጦር መሪዎችን ማባረራቸውም የዕቅዳቸው አንዱ አካል መሆኑን ገልጿል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ከስልጣናቸው ያባረሯቸው የጦር መሪዎች፡- ማርሻል አሌክስ ባዴህ፣ ሜጀር ጄኔራል ኬንዝ ሚናማህ፣ ሪር አድሚራል ኡስማን ጂብሪንና ምክትል ማርሻል አዴሶላ አሞሱ ናቸው ተብሏል፡፡
በምርጫው አሸንፈው ስልጣን ከያዙ፣ የመጀመሪያ ተልዕኳቸው የሚያደርጉት ቦኮ ሃራምን መደምሰስ እንደሆነ ሲገልጹ የነበሩት ቡሃሪ፣ ግንቦት ወር ላይ ስልጣን ከተረከቡ በኋላ፣ የአገሪቱን የመከላከያ ዕዝ መቀመጫ የአሸባሪ ቡድኑ መፈጠሪያ ናት ወደምትባለው ሜዱጉሪ ማዛወራቸውንና፣ ቡኮሃራምን ለመደምሰስ ያለመውን የአገራት ጥምር ሃይል ማዘዣ ጣቢያም በቻድ መዲና ጃሜና ማቋቋማቸውንም ዘገባው ጠቁሟል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

  “...አንዳንድ እርእሶችን ዝም ብለን ሸፋፍነን የምናልፍባቸው ግዜያት አሉ፡፡ ምክንያቱም ጠለቅ ብለን ካወራን ቤተሰቦች ሌላ ነገር ሊያስቡ ይችላሉ፡፡”
“...የወርአበባዬ የመጣ የመጀመሪያ ቀን... በጣም ነበር የደነገጥኩት አስቀድማ እናቴ ብትነግረኝ ኖሮ... ላልደነግጥ እችል ነበር፡፡ ስነግራት አደግሽ ማለት እኮ ነው ...ብቻ ነበር ያለችኝ”
ከላይ ያነበባችሁት ለዚህ እትም የተጋበዙት እንግዶች ከተናገሩት እውነታ የተወሰደ ነው፡፡ ሌላ እውነታም ታነቡ ዘንድ እነሆ...   
ልጅቷ ከትምህርት ቤት የተሰጣትን የቤት ስራ ይዛ ወደ እቤት ተመልሳለች፡፡ እቤት ስትደርስ ያገኘችው ታላቅ እህቷን ነበር፡፡ ወዲያው “የወር አበባ ምንድነው?” አለቻት ጮክ ብላ በነጻነት...፡፡ እንዳሰበችው ለጥያቄዋ መልስ ሳይሆን ጥፊ ነበር ያገኘችው፡፡ ጥፊ ያደነዘዘውን ጉንጯን በእጇ ይዛ “ጠይቁ ተብለን እኮ ነው” አለች እያለቀሰች፡፡ እህት ነገሩን በዝምታ ለማለፍ ብትሞክርም ልጅት ቀጥላለች “እሺ ጋሼን ብጠይቀው ይነግረኛል?” አባቷን ማለቷ ነበር፡፡ “...ሁለተኛ ከሰው ፊት እንዲህ ብለሽ ስታወሪ እንዳልሰማሽ...” ከባድ ማስጠንቀቂያ ከሌላ ዱላ ጋር...፡፡ ለካስ የቤት ስራው ይህ ነበር፡፡ የአካባቢ ሳይንስ መምህራቸው “የወርአበባ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ቤተሰቦቻችሁን ጠይቃችሁ እንድትመጡ፡፡” ብሎ ነበር። እሷም እንደታዘዘቸው ነበር ያደረገችው ያላሰበችው ዱብእዳ ገጠማት እንጂ፡፡
ታሪኩ ይህን ፅሁፍ ሳዘጋጅ የስራ ባልደረባዬ “የመጨረሻ ልጄ የቤት ስራ” ብላ ያጫወተችኝ ነው። ምናልባትም ይህ የብዙዎቻችን ገጠመኝ ሊሆን ይችላል። ስንቶቻችን ነን በስነተዋልዶ ጤናም ይሁን በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ለምናነሳቸው ጥያቄዎች ትክክለኛ መልስ እያገኘን ያደግን? ምላሻችሁን መገመት አያዳግትም፡፡      
በተለያየ ግዜ የተደረጉ ጥናቶች ወላጆች በስነተዋዶጤና ጉዳዮች ላይ ከልጆቻቸው ጋር ግልፅ የሆነ ውይይት ለማድረግ ምቾት እንደማይሰማቸው እና ይህን ለማድረግም ያላቸው ተነሳሽነት ዝቅተኛ እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ወጣቶች በተገቢው ግዜ ማግኘት የሚገባቸውን ትምህርት ወይም ደግሞ መረጃ ሳያገኙ ይቀራሉ፡፡
ለዚህ እንደ ምክንያት ከሚጠቀሱት ነገሮች መካከል ወላጆች ይህን መሰል ጉዳዮችን የማሳወቅ ግዴታ የትምህርት ቤቶች ነው ብለው በማሰባቸው እንደሆነ በተደጋጋሚ ይነሳል፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን የስነተዋልዶ ጤናን እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ትምህርቶችን ለልጆች ለመስጠት ወላጆች ወይንም ቤተሰቦች በጣም ቅርብ መሆናቸው እሙን ነው፡፡
ወንዶችም ሆኑ ሴት ልጆች የስነተዋልዶ ጤና ላይ በቂ እውቀት እና ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ነገር ግን ሴቶች ከወንዶች በተለየ መልኩ የተለያዩ አካላዊ ለውጦችን ስለሚያስተናግዱ፤ እንዲሁም የዛሬ ሴት ልጆች የነገ እናቶች በመሆናቸው በዚህ ዙሪያ ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡
በጉርምስና ግዜ የሚከሰት አከላዊ እድገትን እና የባህሪ ለውጦችን፣ ወሲባዊ ግንኙነት በሰዎች ህይወት ውስጥ የሚኖረውን ቦታ እንዲሁም ሌሎች ጤና ነክ ጉዳዮች ለውይይት ቀርበው ወጣቶች በቂ ግንዛቤ ሊያገኙባቸው ከሚገቡ ጉዳዮች መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡
ለዚህ እትም ከጋበዝናቸው ወጣቶች መካከል አንድዋ ሰራዊት ትባላለች፡፡ ሰራዊት በአስራዎቹ የእድሜ ክልል ላይ የምትገኝ ታዳጊ ነች፡፡
ከቤተሰቦቿ ጋር ጥሩ የሚባል ግንኙነት እንዳላት እና በማንኛውም ጉዳይ ላይ ግልፅ ውይይት እንደሚያደርጉ ትመሰክራለች፡፡ ይህ የሆነው “ግልፅነት በእኛ ቤተሰብ ውስጥ ያለ እና እንደ ባህል የያዝነው ነገር ስለሆነ ነው” ትላለች፡፡ “በይበልጥ  ከአባቴ ጋር  ነው የምናወራው። እቤታችን ውስጥ ግልፅ ውይት ስላለ ለእኔ ያን ያህል ከባድ አይደለም፡፡” ይሁን እንጂ... ግልፅ ውይይት ቢያድርጉም የውይይት እርእሶቹ በእጅጉ የተገደቡ እንደሆኑም አልሸሸገችም፡፡
“...አንዳንድ እርእሶችን ዝም ብለን ሸፋፍነን የምናልፍባቸው ግዜያት አሉ፡፡ ምክንያቱም ጠለቅ ብለን ካወራን ቤተሰቦች ሌላ ነገር ሊያስቡ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ወሲብ ነክ ጥያቄዎችን በምትጠይቂበት ግዜ ወላጆች ነገሩን ያደረግሽው ወይም ለማድረግ ሀሳብ እንዳለሽ ሊያስቡ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ እኔም ደፍሬ አልጠይቅም እነሱም ይህን ጉዳይ አያነሱትም፡፡”
ሌላዋ ወጣት ሜሮን ትባላለች፡፡ ሜሮን የ22 አመት ወጣት ነች፡፡ አሁን ላይ ሜሮን የስነተዋልዶ ጤና ጉዳዮችን በሚመለከት ያላት ግንዛቤ በቂ የሚባል እንደሆነ ትናገራለች፡፡ ነገር ግን ይህ ከቤተሰቦቿ ጋር በምታደርገው ውይይት የመጣ ሳይሆን ከትምህርት ቤት እንዲሁም በግል ከተለያዩ መረጃዎች ያገኘሁት ነው ትላለች፡፡
“በእኛ ቤተሰብ ውስጥ በዚህ ጉዳይ ላይ ውይይት ብሎ ነገር ኖሮ አያውቅም፡፡ እኔም ሆንኩ እህቶቼ ብዙውን ነገር ያወቅነው ከትምህርት ቤት እና ከተለያዩ መረጃዎች ነው፡፡ አስታውሳለሁ ...የወርአበባዬ የመጣ የመጀመሪያ ቀን በጣም ነበር የደነገጥኩት፤ ይህ ነገር እንደሚፈጠር አስቀድማ እናቴ ብትነግረኝ ኖሮ ምናልባት ያን ያህል ላልደነግጥ እችል ነበር፡፡ ከሆነ በኋላ እንኳን ስነግራት አደግሽ ማለት እኮ ነው ብቻ ነበር ያለችኝ”  
በሀገራችን ከቤተሰብ ወይም ከአሳዳጊ ጋር ይህን መሰል ውይይቶችን ማድረግ የተለመደ አይደለም። ውይይት ለማድረግ ሀሳብ ይሰጣል ያልነውን መረጃ ለንባብ ብለናል፡፡
//////////////////////////////
በስነተዋልዶ ጤና ዙሪያ  ወላጆች እና ልጆቻቸው የሚኖራቸውን ግንኙነት እንዴት ማጠንከር ይቻላል?
ብዙ ወላጆች የስነተዋልዶ ጤናን የተመለከቱ ጉዳዮችን ከልጆቻቸው ጋር በግልፅ ለመወያየት ከባድ ሲሆንባቸው ይስተዋላል፡፡ ነገርግን በቤተሰብ ውስጥ ይህ አይነቱ ውይይት እንዲኖር ለማድረግ የሚረዱ መንገዶች አሉ፡፡
እናቶች ለልጆቻቸው በእጅጉ የቀረቡ እና የስነተዋልዶ ጤናን በተመለከተ የሚኖሩትን አካላዊውም ሆነ ስነልቦናዊ ጉዳዮችን ከልጆቻቸው ጋር ለመወያየት ዝግጁ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡
እናቶች ከወንዶችም ሆነ ከሴት ልጆቻቸው ጋር የቀረበ ግንኙነት መፍጠር እና ልጆቻቸው ነፃነት እንዲሰማቸው ማድረግ አለባቸው፡፡
ወላጆች የስነተዋልዶ ጤናን በተመለከተ በሚኖሩት ውይይቶች ላይ ሴቶችም ሆኑ ወንዶች ልጆቻቸው እንደ የወር አበባ ባሉ የስነተዋልዶ ጉዳዮች ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ስኬታማ ውይይቶች
አንዳንድ ቤተሰቦች ስነተዋልዶ ጤናን እንዲሁም ወሲብ ነክ ጉዳዮችን በተመለከተ ከልጆቻቸው ጋር ግልፅ የሆነ ውይይት ያደርጋሉ፡፡ ይህም የሚከተሉትን ሁኔታዎች ያካትታል፡-
ወላጆች ጥሩ አድማጭ መሆን
ወላጆች ልጆቻቸው ለሚያነሱላቸው ጥያቄዎች በቂ እና ታአማኒ ምላሾችን መስጠት
በውይይት ወቅት ልጆች የግል አመለካከታቸውን ያለ ምንም ተፅእኖ እንዲናገሩ መፍቀድ
ልጆች ጥብቅ የሆነ መመሪያ እንዲከተሉ ከማድረግ ይልቅ ቀርቦ ውይይት በማድረግ ሀሳብ ማቀበል
ይህ ሲሆን ልጆች በወላጆቻቸው ዘንድ ተሰሚነት እንዳላቸው እና ወላጆቻቸው ከጎናቸው እንደሆኑ ያስባሉ።
ውይይቱን የሚያውኩ ነገሮችን ማስወገድ
አንዳንድ ሁኔታዎች ውይይቱን ሊያውኩ እና ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ሊመሩት ይችላሉ፡፡ በውይይት ወቅት መወገድ ከሚገባቸው ሁኔታዎች መካከል፡-
ልጆ ከእርሶ ጋር ተመሳሳይ አቋም እንዲኖረው አለመጠበቅ
የያዙት ሀሳብ ትክክል ባይሆን በትእግስት ለማስረዳት መሞከር
ሀሳባቸውን ከመተቸት መቆጠብ ወይም አለመቆጣት
በንግግራቸው መሀል ጣልቃ አለመግባት
በጥሞና ማዳመጥ
ሁልግዜ የእርሶ መመሪያ እና ክትትል እደሚያስፈልጋቸው አለማሰብ “ምክሮ እንደሚያስፈልጋቸው ቢሰማዎት እንኳን አስቀድመው ምክንያቱን መንገር ይኖርቦታል።”
ወሲብ ነክ ጥያቄዎች ሲቀርብሎት ስለልጆ መጥፎ ወይም የተሳሳተ አመለካከት መያዝ የለቦትም፡፡ ቁጣ የተቀላቀለበት ምላሽ ልጆችዎ ዳግመኛ ተመሳሳይ ጥያቄዎችን እንዳያነሱ ሊያደርጋቸው ይችላል፡፡
ምንጭ፡-  Better health channel

Published in ላንተና ላንቺ

 ለቤጂንግ 44 አትሌቶች ያሉበት የኢትዮጵያ ጊዜያዊ ቡድን ታውቋል
                               
           9ኛው የዓለም ታዳጊዎች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በኮሎምቢያዋ ከተማ ካሊ ባለፈው ሐሙስ ሲጀመር ኢትዮጵያ የመጀመርያ የወርቅ ሜዳልያዋን በ3ሺ ሜትር በማስመዝገብ ጥሩ አጀማመር አሳይታለች። የወርቅ ሜዳልያውን ያገኘችው አትሌት ሹሩ ቡሎ ስትሆን በ3ሺ ሜትር ሴቶች ያሸነፈችው የሻምፒዮናውን ፈጣን ሰዓት በ9 ደቂቃዎች  ከ01.12 ሰከንዶች አስመዝግባ ነው፡፡ በሻምፒዮናው ኢትዮጵያ 10 ሴትና 10 ወንዶች ባካተተ ቡድኗ የምትሳተፍ  ሲሆን ሻምፒዮናው ነገ ሲጠናቀቅ ቢያንስ  9 ሜዳልያዎች ሶስት ወርቅ፤ 3 የብርና 3 የነሐስ እንደምትሰበስብ ግምት አለ፡፡ በዓለም የታዳጊዎች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያን በሁለቱም ፆታዎች የወከሉት 20 አትሌቶች አሰላ ላይ ለሶስተኛ ጊዜ በተደረገው የታዳጊዎች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በመሳተፍ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ መሆናቸውን ያስታወቀው ፌደሬሽኑ የወደፊት የአገሪቱን ኮከብ አትሌቶች ለማግኘት ዓለም አቀፍ ውድድሩ ወሳኝ እንደሆነ አምኖበታል። በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር የሚዘጋጀው የዓለም ታዳጊዎች አትሌቲክስ ሻምፒዮናው በየሁለት ዓመቱ ሲካሄድ በ16 እና 17 ዓመት የእድሜ ክልል የሚገኙ አትሌቶች በሁለቱም ፆታዎች በ40 የውድድር መደቦች ይሳተፉበታል።  ከ800 እስከ ሁለት ሺህ ሜትር  የሩጫና እርምጃ  ውድድሮች የሻምፒዮናው አካል ናቸው፡፡ ከ2 ዓመታት በፊት በዩክሬኗ ከተማ ዶኔትስክ ላይ ተደርጎ በነበረው 8ኛው የዓለም ታዳጊዎች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የኢትዮጵያ ቡድን  ሶስት የወርቅ፣ ሶስት የብር እና ሁለት የነሐስ ሜዳሊያ በመሰብሰብ ከዓለም ሶስተኛ ከአፍሪካ ደግሞ ሁለተኛ ደረጃ ይዞ ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡
በተያያዘ ከወር በኋላ በቻይናዋ ከተማ ቤጂንግ ለሚደረገው 15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን ለሚወክለው ቡድን የተመለመሉ አትሌቶች  ጊዜያዊ ስም ዝርዝርን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ኮሙኒኬሽን ክፍል አስታወቀ።  በነሐሴ ወር አጋማሽ  በሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው ላይ ኢትዮጵያ በ800 እና 1500 ሜትር መካከለኛ ርቀት፤ በ3ሺ ሜትር መሰናክል፤ በረጅም ርቀት 5ሺ እና 10ሺ ሜትር እንዲሁም በማራቶን ውድድሮች በምትሳተፍበት ቡድን 44 አትሌቶች በጊዜያዊ ስም ዝርዝሩ ገብተዋል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ኮሙኒኬሽን ክፍል ሐምሌ 9/2007 ዓ. ም. ይፋ ያደረገው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ ቡድን ጊዜያዊ ቡድን የአትሌቶች  ስም ዝርዝር ከዚህ በታች የቀረበው ነው፡፡
በ800 ሜትር በወንዶች መሃመድ አማንና ጀና ኡመር እንዲሁም በሴቶች ሃብታም አለሙ፣ ባይህ ጫልቱ ሹሜ ረጋሳና ኮሬ ቶላ ነገሆ
በ1500  ሜትር በሴቶች ዳዊት ስዩም ፣ ሰንበሬ ተፈሪ ፣አክሱማዊት እምባዬና ጉዳፍ ፀጋዬ እንዲሁም በወንዶች ሱር አማን ወጤ እና መኮንን ገ/መድህን
በ5 ሺ ሜትር ዘጠኝ እንዲሁም በ10ሺ ሜትር ስምንት አትሌቶች በሁለቱም ፆታዎች በጊዜያዊ ዝርዝሩ ተካትተዋል፡፡ በ5ሺ ሜትር ወንዶች ዮሚፍ ቀጀልቻ፣ ሐጐስ ገ/ህይወት ደጀን ገ/መስቀልና የኔው አላምረው ሲሆኑ በሴቶች ደግሞ  አልማዝ አያና፣ ገንዘቤ ዲባባ፣ ሰንበሬ ተፈሪ፣ አለሚቱ ሃዊ  አዝመራ ገብሩ
በ10 ሺ ሜትር ወንዶች ሙክታር አድሪስ፣ ኢማነ መርጊያ፣ ሞስነት ገረመውና  አዱኛ ታከለ፤ በሴቶች ደግሞ ገለቴ ቡርቃ፣ አለሚቱ ሃሮዬ ፣በላይነሽ ኦልጅራ እና  ማሚቱ ዳስካ
በ3000 ሜትር መሠናክል በሁለቱም ፆታዎች ስምንት አትሌቶች ሲያዙ በሴቶች ሕይወት አያሌው፣ ሶፊያ አሰፋ፣ ብርቱካን ፋንቴና ትዕግስት ጌትነት  እንዲሁም በወንዶች ጂክሳ ቶሎሳ፣ ኃ/ማርያም አማረ፣   ታፈሰ ሰቦቃና  ጫላ በዩ
በማራቶን በሴቶች   ትርፌ ፀጋዬ፣ ማሬ ዲባባ፣ ትዕግስት ቱፋ፣ ብርሃኔ ዲባባ  ተይዘው፤ በወንዶች ደግሞ ሌሊሳ ዲሳሳ ፣ የማነ ፀጋዬ፣ ለሚ ብርሃኑ እና እንደሻዉ ካሳ

ጥርስ ድህነት አይታየውም፡፡
የማሳዮች አባባል
ትዕግስት ከሌለህ ቢራ መጥመቅ አትችልም።
የአቫምቦ አባባል
የእንቁላል ቅርጫት ተሸክመህ አትደንስ፡፡
የአምቤዴ አባባል
የአይጥ ልጅ አይጥ ናት፡፡
የማላጋሲ አባባል
ላልተወለደ ልጅ ስም ማውጣት አትችልም።
የአፍሪካውያን አባባባል
በሽምግልናህ የተቀመጥክበት ቦታ በወጣትነትህ የቆምክበትን ቦታ ያሳያል፡፡
የዩሩባ አባባል
የሚሸሽን ሰው አትከተለው፡፡
የኬንያውያን አባባል
ቤት ስታንፅ ምስማሩ ቢሰበርብህ፣ ማነፁን ትተወዋለህ ወይስ ምስማር ትቀይራለህ?
የሩዋንዳውያን አባባል
እናቱ የሞተችበት ጥጃ የራሱን ጀርባ ይልሳል።
የኬንያውያን አባባል
ንዴትና እብደት ወንድማማች ናቸው፡፡
የአፍሪካውያን አባባል
አንዲት ደስታ መቶ ሃዘኖችን ታዳብራለች፡፡
የቻይናውያን አባባል
 ፍቅር ለአሉባልታ ጆሮ የለውም፡፡
የጋናውያን አባባል
ሙሉ ጨረቃ ከወደደችህ፤ የክዋክብቶቹ ለምን ያስጨንቅሃል?
የቱኒዚያውያን አባባል

Published in ከአለም ዙሪያ

   ከሳምንት በፊት በዱዋላ ከተማ  በአፍሪካ የሀ20 ዓለም ዋንጫ የመጀመርያ ዙር ማጣሪያ ጨዋታየካሜሮን አቻውን በመግጠም 0ለ0 በሆነ አቻ ውጤት የተለያየው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከትናንት በስቲያ አዲስ አበባ በሰላም ገብቷል፡፡ ከሜዳው ውጭ ግብ ሳይቆጠርበት ነጥብ ተጋርቶ ለመውጣት የቻለው ቡድኑ ከሳምንት በኋላ በመልስ ጨዋታው በሜዳው ተጋጣሚውን ሲያስተናግድ በማናቸው ውጤት ማሸነፍ ከቻለ ወደ ሁለተኛ ዙር የማጣርያ ምእራፍ ይገባል፡፡ በተያያዘ የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከዱዋላው  ጨዋታ በኋላ ወደ አገሩ ለመመለስ ለ3 ጊዜያት በገጠመው የበረራ ጉዞ መስተጓጎል እና መጎሳቀል የካሜሮን አየር መንገድ ዋንኛ ተጠያቂ መሆኑን የእግር ኳስ ፌደሬሽን የህዝብ ግንኙነት ዓላፊ የሆኑት አቶ ወንድምኩን አላዩ ለስፖርት አድማስ ገልፀዋል፡፡  በሁሉም ደረጃ ላሉ ብሄራዊ ቡድኖች ከአገር ውጭ በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች የተለያዩ የጉዞ ዝግጅቶችን የፌደሬሽኑ የህዝብ ግንኙነትና የፕሮቶኮል ክፍሎች በጥምረት እንደሚያከናውኑት የገለፁት አቶ ወንድምኩን፤ በካሜሮን ያጋጠመው እንግልት የእግር ኳስ ፌደሬሽኑን በጣም  አስቀይሞታል ብለዋል፡፡ ይህን በማስመልከትም ለአህጉሪቱ እግር ኳስ አመራር አካላት በደብዳቤ ዝርዝር ቅሬታውን እንደሚያቀርብም ገልፀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን እና ልዑካኑ  በካሜሮን አየር መንገድ  ሶስት የተስተጓጎሉ በረራዎች በአየር ማረፊያ ተጎሳቅለው ያሳለፉበትን ምክንያት  አቶ ወንድምኩን አላዩ ሲያብራሩ፤ ከአየር ማረፊያው ወጥቶ በሆቴል ለማደር ያልተቻለው የልዑካን ቡድኑ ለ3 ጊዜያት ቦርዲንግ ፓስ አስጨርሶ ወደ ውጭ መውጣት ወደማይቻልበት  ክፍል እየገባ አውሮፕላኖቹ በመቅረታቸው የተፈጠረ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የካሜሮን አየር መንገድ የአውሮፕላን እና የሰራተኛ እጥረት እንዳለበት በተደጋጋሚ ባደረግናቸው የጉዞ አጋጣሚዎች የታዘብነው ነው ያሉት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊው፤ በኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ላይ ለ3 ቀናት በፈጠረው መጉላላት በነፍስ ወከፍ በቀን ከ200 እሰከ 300 ዶላር ወጭ ያደርጋል ብለዋል፡፡የኢትዮጵያን እግር ኳስ በመወከል ከአገር ወጥተው በተለያዩ ግጥሚያዎች በሚሳተፉ የብሄራዊ እና የክለብ ቡድኖች ላይ በየጊዜው የሚያጋጥሙት መጉላላላቶች እና የመስተንግዶ ችግሮች መቀጠል እንደሌለባቸው የፌደሬሽኑ እምነት ነው ያለው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊው አቶ ወንድምኩን አላዩ፤ የገጠሙ ችግሮችን አስመልክቶ ለጨዋታው ኮሚሽነሮች በዝርዝር ሪፖርት አቅርበናል ብለው፤ በቀጣይ ካፍ እና አመራር አካላቱ  በምናስገባው የቅሬታ ማመልከቻ ዘላቂ እርምት እንዲፈጠር እንጠይቃለን ብለዋል፡፡ የብሔራዊ ልዑካን ቡድኑ 18 ተጨዋቾች፣ የህክምና፣ የቡድን መሪ፣ የማሳጅ፣ አሰልጣኝና የመረጃ ባለሙያን ጨምሮ 26 አባላትን ያካተተ ነበር፡፡
በአሰልጣኝ አስራት አባተ የተመራው ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከካሜሮን ጋር ነጥብ ተጋርቶ መውጣቱ የመልሱ ጨዋታ ያቀልለታል፡፡ ሙሉ ቡድኑ በካሜሮን በተፈጠረው መጉላላት ሞራሉ ሳይዳከም በከፍተኛ መነቃቃት ልምምዱን እስከመለስ ጨዋታው እንደሚቀጥል የፌደሬሽኑ ህዝብ ግንኙነት ጨምሮ ገልጿል፡፡ የመልስ ጨዋታው ከሳምንት  በኋላ ሲካሄድ የመጋጠሚያው ቦታ በአዲስ አበባ ወይንም በባህርዳር ስታድዬም እንደሆነ አልታወቀም፡፡ የኢትዮጵያ እና የካሜሮን ከ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን አሸናፊ በቀጣይ ዙር ማጣርያው የሚገናኘው ከአልጄርያ ወይንም ከብሩንዲ አሸናፊ ጋር ይሆናል፡፡ የቡርኪናፋሶ ቡድን በመጀመርያ ጨዋታው ከሜዳው ውጭ አልጄርያን 2ለ1 አሸንፏል፡፡ ከዚሁ የማጣርያ ምዕራፍ በኋላ የመጨረሻው 3ኛ ዙር ማጣርያ ሲደረግ በደርሶ መልስ ጥሎ የሚያልፍ ቡድን  በ2016 በፓፓዋ ኒው ጊኒ አዘጋጅነት በሚካሄደው ከ20 ዓመት በታች የሴቶች የዓለም ዋንጫ ተሳታፊነቱን ያገኛል፡፡

ዘንድሮ በአሜሪካዋ ከተማ ዩጂን የሚገኝ ክለብን በመቀላቀል ተቀማጭነቱን በዚያው ያደረገው አትሌት መሃመድ አማን በቤጂንግ የዓለም ሻምፒዮና ክብሩን የማስጠበቅ ፍላጎት እንዳለው አስታወቀ፡፡
መሃመድ አማን ሰሞኑን ስፓይክስ በተባለ የአትሌቲክስ ድረገፅ ላይ የአማን ዓለም በሚል በወጣ ዘገባ  በረጅም ርቀት ታላላቅ አትሌቶች ትታወቅ የነበረችው ኢትዮጵያን በ800 ሜትርም ምርጥ አትሌቶች ለማፍራት አቅም እንዳላት ያሳየ አትሌት ተብሎ ተደንቋል፡፡
በስፓይክ መፅሄት ዘገባ ላይ መሃመድ በሰጠው አስተያየት ‹‹አሰልጣኜ፤ አባቴም ሳይቀር በ5ሺ እና በ10ሺ መሮጥ እየቻልክ ለምን በ800 እየሮጥክ ግዜህን ታባክናለህ ይሉኝ ነበር›› ብሎ  ‹‹ ሁሌም ግን በመካከለኛ ርቀት እንደሚሳካልኝ በማመን ባደረግኩት ጥረት  እንደሚሳካልኝ አልጠራጠርም ነበር›› ሲል ተናግሯል፡፡ የ21 ዓመቱ አትሌት መሃመድ አማን፤ ተቀማጭነቱን በአሜሪካ ካደረገ በኋላ ስልጠናው እና ኑሮውን እየለመደ መምጣቱን የገለፀው ስፓይክ መፅሄት አሜሪካ መኖር ከጀመረ በኋላ በአሜሪካ ፉትቦል እና ቅርጫት ኳስ ስፖርቶች መማመረክ መጀመሩንም አትቷል፡፡በአይኤኤኤፍ የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች በሁለት የውድድር ዘመናት አሸናፊ በመሆን  ከፍተኛ ትኩረት ከሚያገኙ አትሌቶች አንዱ የሆነው መሃመድ አማን ዘንድሮ በርቀቱ ለሱስተኛ ጊዜ ለማሸነፍ ሰፊ እድል እንዳለው ይገለፃል፡፡ በዩጂን እና በሮም የተደረጉ የዳይመንድ ሊግ ውድድሮችን በማሸነፍም ግምቱን ለማሳካት በጉዞ ላይ ነው፡፡
አትሌት መሃመድ ፤ በ800 ሜትር ሶስት የዓለም ሻምፒዮንነት ክብሮች ሲኖሩት ሁለቱ በዓለም የአትሌቲክስ የቤት ውስጥ ውድድር የተመዘገቡ እንዲሁም ዋንኛው ደግሞ ከሁለት ዓመት በፊት በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ800 ሜትር የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ ሻምፒዮን ለመሆን የበቃበት ናቸው፡፡ በ800 ሜትር የኢትዮጵያ ሪከርድን የጨበጠው መሃመድ አማን በርቀቱ 9ኛ ደረጃ ላይ የሚቀመጠውን የምንግዜም ፈጣን ሰዓትም አስመዝግቧል፡፡ በ800 ሜትር ፈጣን ሰዓቱ 1 ደቂቃ ከ42.37 ሰከንዶች ነው፡፡
እንደ ስፓይክ መፅሄት ሀተታ መሃመድ አማን አሁን ትኩረቱ በቤጂንግ በሚደረገው 15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ800 ሜትር  የሻምፒዮንነት ክብሩን በማስጠበቅ በውድድሩ ታሪክ ሶስተኛው ሰው የመሆን ፍላጎቱን ማሳካት ነው፡፡ በዓለም ሻምፒዮና ታሪክ በ800 ሜትር አከታትለው የወርቅ ሜዳልያ የወሰዱት ሁለት አትሌቶች  ብቻ ሲሆኑ ቢሊ ኮንቼላህ እና ኬንያዊው ዊልሰን ኪፕኬተር ናቸው፡፡

   በአብያታና ሻላ ሃይቆች በሚገኙት ፓርኮች እና ተራራማ ስፍራዎች የሚካሄደው የኢትዮትሬል የተራራ ላይ ሩጫ ውድድር እድገት በማሳየት ከወር በኋላ እንደሚካሄድ ታወቀ፡፡ ለሯጮች፤ ለተራራ ወጪዎች እና ተጓዦች እንዲሁም ሙሉ ቤተሰብ  አሳታፊ ለሆኑት የኢትዮትሬል  ውድድሮች የዓለም አቀፍ ተሳታፊዎች ጉጉት አስደናቂ ሆኗል፡፡  ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ በሚካሄደው  የኢትዮ ትሬል የተራራ ላይ ሩጫ በሶስት ርቀቶች በ42፤ በ21 እና 12 ኪሎሜትሮች ተካፋፍሎ እንደሚካሄድ አዘጋጆቹ ለስፖርት አአድማስ በላኩት መግለጫ አመልክተዋል፡፡ የተራራ ላይ ሩጫው በኢትዮጵያ የስፖርት ቱሪዝምን ለማስፋፋት እና ጤናማ አኗኗርን ለማበረታታት የሚዘጋጅ ነው፡፡ ዘንድሮ በዓለም አቀፉ የትራያል ሩጫ ማህበር አባልነት የተመዘገበው ኢትዮትሬል ከዓለም 50 መሰል ሩጫዎች አንዱ ሆኖም ተጠቅሷል፡፡ ባለፈው ዓመት ውድድሩ ሲካሄድ ከአገር ውስጥ እና ከባህርማዶ እስከ 300 ተሳታፊ ስፖርተኞች እና 2000 ተመልካቾች የነበሩት ሲሆን ዘንድሮ የተሳታፊዎቹን ቁጥር ወደ 800 እንደሚያሳድግና ታዳሚዎቹም ከ3ሺ በላይ እንደሚሆኑ ተጠብቋል፡፡

Page 6 of 17