ከ50 በላይ የዓለም መሪዎች፣ ከ100 የሚበልጡ የአገራት ሚኒስትሮች፣ ከ2ሺ በላይ የቢዝነስ ሃላፊዎች… በአጠቃላይ ከ5ሺ -7ሺ የሚደርሱ የዓለም ህዝቦች ከሰኞ ጀምሮ ለ4 ቀናት በአዲስ አበባ ላይ ከትመው ሲወያዩ ሰንብተዋል፡፡ 3ኛው ዓለምአቀፍ የፋይናንስ ፎረም ለልማት በመዲናዋ በመካሄዱ ኢትዮጵያ የቱን ያህል በምን ረገድ ተጠቀመች? ከፎረሙ ተሳታፊዎች አንዱ የነበሩትና በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ዙሪያ በሸራተን አዲስ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት    የ “ኤርነስት ኤንድ ያንግ ኢትዮጵያ” ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ፤ በተለያዩ ጉባኤዎች ከተወጣጠረ ጊዜያቸው ላይ ቀንሰው በስልክ ላቀረብንላቸው ጥቂት ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተውናል፡፡



ኢትዮጵያ ሰሞኑን በመዲናዋ ከተካሄደው ጉባኤ ምን ተጠቀመች?
ይሄ ለኢትዮጵያ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ጉባኤ ነው፡፡ ይሄን ሁሉ እንግዳ ማስተናገድ በራሱ ለሃገሪቱ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ ብዙ የአፍሪካ ሃገሮች ይሄን አይነት ጉባኤ የማስተናገድ አቅሙ የላቸውም፡፡ የሆቴሎች እንዲሁም መሰረተ ልማቶች እንዲሁም የፀጥታ ችግር ሃገራትን እንዲህ አይነቱ ጉባኤ ይፈታተናቸዋል፡፡ በዚህ ጉባኤ  ከ5 ሺህ - 7 ሺህ የሚደርስ የዓለም ህዝብ እንደታደመ ይገመታል፡፡ ይህን የሚያህል ህዝብ ማስተናገድ የሚችሉ ከተሞች በዓለም ላይ በጣም ትንሽ ናቸው፡፡ በአፍሪካ ቢበዛ ከሁለት አይበልጡም፡፡
ሌላው ስብሰባው አዲስ አበባ ውስጥ በመደረጉ ብዙ ሰዎች የሃገሪቱን እንቅስቃሴ ይመለከታሉ። ከተፃፈው በተጨማሪ በዓይናቸው ሲመለከቱ፣ ይበልጥ ትኩረት እንዲሰጡት ያደርጋቸዋል፡፡ ትልልቅ ድርጅቶች እና ኩባንያዎች ይበልጥ በሃገሪቱ አጠቃላይ ሁኔታ እንዲሳቡ እድል ይፈጥራል። በዚህ ስብሰባ ላይ ታላላቅ የዓለም መሪዎች፣ የቢዝነስ ሃላፊዎች በመገኘታቸው ለኢትዮጵያ በጣም እንደሚጠቅም ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በአጋጣሚው ተጠቅማ ምን ያህል ራሷን ለዓለምአቀፉ ማህበረሰብ መግለጽና ማስተዋወቅ ቻለች?
ለምሳሌ ማክሰኞ እለት በሸራተን “ኢትዮጵያ ራይዚንግ” የተሰኘ ኮንፈረንስ ተካሂዶ ነበር፡፡ በከፍተኛ ደረጃ ያሉ ሰዎች ናቸው የመሩት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ስለ ኢትዮጵያ ፖሊሲ አብራርተዋል፡፡ የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንትም ስብሰባው ላይ ነበሩ። የኛም ድርጅት (ኤርነስት ኤንድ ያንግ) ኢትዮጵያ ውስጥ መዋለ ንዋይን ለማፍሰስ የሚያስችሉ 10 ምክንያቶች በሚል ገለፃ አድርጓል፣ የተለያዩ ሪፖርቶችም ቀርበዋል፡፡ ስለ ኢትዮጵያ ብቻ ከ2 ሰዓት በላይ ታላላቅ የዓለም ሰዎች በተገኙበት ሰፊ ማብራሪያና ገለፃ ተደርጓል፡፡
ከፎረሙ ጋር በተገናኘ አገሪቱ በገቢ ደረጃ ምን ያህል እንደምታገኝ ተብሎ ይገመታል?
በተለያየ መንገድ ነው የሚታየው፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ያሉ ሆቴሎች በሙሉ ሙሉ ናቸው፡፡ አንድ ጥናት እንዳረጋገጠው፤ ከትንሽ ጀምሮ እስከ ትልቅ ሆቴል ድረስ የአልጋ ቁጥሩ ወደ 5ሺህ ይደርሳል። ስለዚህ በከተማው ያሉ ለቱሪስት መጣኝ የሆኑ ሆቴሎች በሙሉ ሙሉ ናቸው ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል የመጣው ሰው ሁሉ በየሬስቶራንቱ ይበላል፣ በምሽት ይዝናናል፣ ይገበያያል፣ የቱሪስት ስፍራዎችን ይጎበኛል፡፡ በዚህ ደግሞ ከአየር መንገድ ጀምሮ የመኪና አከራዮች፣ የቱሪስት አስጎብኚዎች ከፍተኛ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ እንዳጋጣሚ ደግሞ የዓለም የቱሪዝም ምርጥ መዳረሻ በሚል መመረጧ የመጡት እንግዶች እንዲጎበኟት ይጋብዛቸዋል፡፡
ከዚህ ተጨማሪ ከፎረሙ በኋላ ጊዜ ወስደው እዚህ ሁለት ቀን ሊቆዩ የሚችሉበትም አማራጭ ይኖራል፡፡ እኔ እስከማውቀው በአፍሪካ ምናልባት ኬፕታውን ነች፣ ከ5 ሺህ በላይ ሰው በአንድ ጊዜ የማስተናገድ አቅም ያለው መሰረተ ልማትና የአገልግሎት ተቋማት ያሏት፡፡ ከእሷ ቀጥሎ አዲስ አበባ ነች ማለት ነው፡፡
ከ10 ቀን በኋላ ደግሞ ፕሬዚዳንት ኦባማ ይመጣል፡፡ ይሄ ማለት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለን ተቀባይነትና እንደ ሃገር ያለን ገፅታ እየተቀየረ መሆኑን ጠቋሚ ነው፡፡ የኦባማ መምጣትም የተለያዩ አገልግሎት ሰጪዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡
በዚህ ፎረም ሆቴሎችና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ምን ያህል ገቢ ሊያስገቡ እንደሚችሉ ይታወቃል? በግምት ደረጃ ማለቴ ነው?
በብዙ ሚሊዮን ዶላር ነው የሚያገኙት፡፡ ሆቴሎች እንኳ ለአንድ አዳር አልጋ ከ200-300 ዶላር በአማካይ ያስከፍላሉ፡፡ ትልልቆቹ እነ ሸራተን፣ ሂልተንና ራዲሰን ደግሞ ከዚህ በላይ ነው፡፡ 5ሺህ ሰው ለ5 ቀን ቢከፍል፣ በዚ ላይ አየር መንገድ በማጓጓዝ የሚያስገባው ገቢ ይኖራል፣ የምግብ፣ የግብይት፣ የቱሪዝም አገልግሎቶች ወዘተ… በሙሉ ሲደማመሩ ሃገሪቱ በብዙ ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ገቢ ታገኛለች፡፡ ኦባማ ሲመጣም እንደዛው ነው፡፡
ሌላው የሚዲያ ሽፋንም ከፍተኛ ነው የሚሆነው። ታላላቅ የዓለም ሚዲያዎች እዚህ ነው ያሉት፤ ፎረሙን በከፍተኛ ደረጃ እየዘገቡት ነው፡፡ ለሃገሪቱ ገፅታ ከፍተኛ ጥቅም ነው ያለው፡፡ ኮንፈረንሱም በአዲስ አበባ ስም ነው የሚሰየመው፡፡

Published in ህብረተሰብ

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ኢድ ሙባረክ!
ሰውየው ጓደኛው ዘንድ ስልክ ደውሎ እንዲህ ይለዋል፡፡ “ምክር ከፈለግህ የጽሁፍ መልእክት ላክልኝ፣ ጓደኛ ከፈለግህ ደውልልኝ፣ እኔን ከፈለግኸኝ ወደ እኔ ና…ገንዘብ ከፈለግህ ግን የደወሉላቸውን ደንበኛ አሁን ማግኘት አይችሉም…” ብሎ ዘጋው፡፡
ስሙኝማ…ጓደኝነት፣ ወዳጅነት ምነዋ እንዲህ ቅጡን አጣ! የምትሰሙት ሁሉ አገር ታምሶ ወዳጅነቶች… ወደ ደመኛ ጠላቶች ስለተለወጡ ‘ቤስት ፍሬንዶች’… ምናምን ሺህ ብር አብሮ አደጉ ስለካደው ምስኪን…ምን አለፋችሁ… “ዓለም የትያትር መድረክ ናት…” የሚለው ላይ…አለ አይደል…ለእኛ አገር “…ያውም የትራጄዲ!” የሚለውን ልትጨምሩ ምንም አይቀራችሁ፡፡
ከምር የሆነ ነገር ነው፡፡ ሰውየው ለሁለት ወር ወርክሾፕ ወደ አንድ አፍሪካ አገር ሄዶላችኋል፡፡ ቤት ውስጥ ከሚስቱ በስተቀር ሌላ ሰው የለም፡፡ እናላችሁ…¸የልብ ጓደኛ ሆዬ የወዳጁ ሚስት ብቻዋን እንዳትሆን በማለት መለስ ቀለስ ሲል ‘አንዱ ነገር ወደ ሌላ እየመራ’ ተቀምጠው የሚያወሩ የነበሩት ጋደም ብለው ‘ወደ መወያየት’ ጀመሩላችሁ፡፡
ሰውየው ተመልሶ ሲመጣ ማን እንደነገረው ሳይታወቅ ጉዱን ይሰማል፡፡ ምንም ሳያቅማማም ፍቺ ጠይቋል አሉ፡፡ የተሻሻለ ዘመን… እንደ በፊቱ ቢሆን ለየጓደኛው እየደወለ… “ስማ አንድ ማካሮቭ ወይም ኮልት ሽጉጥ ምናምን የሚገኝበት ታውቃለህ…” ምናምን ይል ነበር፡፡ እኔ የምለው… እንትናዬዎች ሰይፍ ማማዘዝ ተዉ ማለት ነው!  ቂ…ቂ…ቂ…
ስሙኝማ…በፊት እኮ እንትናዬን ለጓደኛ በአደራ መስጠት ይህን ያህል ስጋት አልነበረውም። እንደውም አንዱ የታማኝ ጓደኛ መገለጫ የዚህን አይነት አደራ መጠበቅ ነው፡፡ የድሮ የልብ ጓደኛ እኮ ጓደኛው ርቆ ሲሄድ እንትናዬውን በአደራ ይጠብቅ ነበር፣ አሁን ግን ጓደኛ በበር ሲወጣ ‘ቤስት ፍሬንድ’ በመስኮት ሳይሆን በዛው በር የሚገባበት ዘመን ነው።
እግረ መንገዴን ይቺን ስሙኝማ፡፡ ሁለቱ ጓደኛሞች ሲጠጡ አምሽተው ዘጠነኛው ደመና ላይ ወጥተዋል፡፡ እናማ… በጨዋታ መሀል ምን ይላል…
“ስማ፣ አንድ የምነግርህ ነገር አለ፡፡ ግን ቅር አይልህም አይደል!”
“ለምንድነው ቅር የሚለኝ! “ስለ ሰው ቀድጄ ልልበሰው…” አይነት ነገር ይናገራል፡፡ ጓደኝየውም…
“ይሄን ስነግርህ አዝናለሁ፡፡ ሚስትህ ግን ለትዳሯ ታማኝ አይደለችም፣” ይላል፡፡ ሰውየው ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው…
“እሷ ሴትዮ በቃ አትሻሻልም! አንተንም ሸወደችህ ማለት ነው?” ብሎት እርፍ፡፡
ቤንጃሚን ፍራንክሊን የሚሉት ሰው… “ሦስት ታማኝ ጓደኞች አሉ፡፡ ያረጀች ሚስት፣ ያረጀ ውሻና፣ በእጅ ያለ ገንዘብ…” ብሏል አሉ ፡፡
ታዲያላችሁ…“የልብ ጓደኛዬ፣ የክፉ ቀኔ…” ምናምን ማለት እያስቸገረ ያለበት ዘመን ነው፡፡
ዘንድሮ ‘ጉድና ጅራት’ ወደኋላ መሆኑ ቀርቶ ፊት ለፊት በሆነበት ዘመን የጥንት የልብ ጓደኛ ማግኘት ደስ ይላል፡፡ ቢያንስ ቢያንስ የሚወራ አይጠፋም። እናላችሁ… እንዲሁ በየኮብልስቶኑ ላይ ዘንበል፣ ዘንበል ስትሉ የጥንት ጓደኛችሁን ታገኛላችሁ፡፡ እናላችሁ ነገርዬው ይሄኔ ነው፡፡
“አንተ! የሚገርም ነው፡፡ አንድ ሀያ ምናምን ዓመት አይሆነንም!” ምናምን እያላችሁ በሰከንድ አሥራ ስምንት ጥይት ትለቃላችሁ፡፡
እሱ ሆዬ… አለ አይደል… መጀመሪያ ትኩር ብሎ ያያችኋል፡፡ ለማስታወስ ግራ የተጋባ ይመስል መልስ ሳይሰጥ ያያችኋል፡፡ እናንተም… “ረሳሁህ እንዳትል…” አይነት ነገር ትሉና “ኮከበ ጽባሀ ሁለተኛ ደረጃ…” ምናምን እያላችሁ መዝገብ መግለጥ ትጀምራላችሁ። አሁንም እንደነገሩ ያያችኋል፡፡ ብዙ ቆይቶ ትዝ ይበለውም፣ አይበለውም…“ኦ!” ይልና ከእጁ ሦስቷን ጣት ያቀረብላችኋል፡፡ እመኑኝ…ይሄ የጥንት ጓደኛችሁ ወይ ገንዘብ አግኝቷል፣ ወይ ወንበር አግኝቷል፡፡ ዘንድሮ ያስቸገሩን ሁለት ነገሮች ቢኖሩ ገንዘብና ወንበር ናቸው፡፡
እናላችሁ… “የጥንት ጓደኛዬ፣ አብረን እኮ ስንትና ስንት አድቬንቸር አሳልፈናል!” አይነት ትዝታ እየጠፋ ነው፡፡
የዘንድሮ ጓደኝነት ደግሞ የሚመሰረተው በአድቬንቸር ምናምን ሳይሆን በገበያው ሁኔታ ነው፡፡ ለጓደኝነት ለመመረጥ ‘በገበያው ላይ’ ያላችሁ ዋጋ መታወቅ አለበት፡፡ እንደ አክስዮን ገበያው ‘ዋጋችሁ’ ዝቅ ሲል “መንገዱን ጨርቅ ያድርግልህ…” ትባላላችሁ፡፡
እናላችሁ…የዘንድሮ ‘ቤስት ፍሬንድነት’ አንጻራዊ ነው፡፡ በቃ ወረቀት ላይ ያልሰፈረ ኮንትራት በሉት፡፡
ሰውየው ምን አለ አሉ መሰላችሁ… “ዕድሜው ከ30 ዓመት በላይ የሆነ ሰውን ምን ያህል ጓደኛ እንዳለው ጠይቀው፡፡ ከአሥር በላይ ብሎ ከመለሰልህ የቆጠረው ጓደኞቹን ሳይሆን የሥራ ባልደረቦቹን ነው፡፡” እንዴት ሸጋ አባባል ነች!
ስሙኝማ…የልብ ጓደኞች የምንባለው እኰ ድሮ የምናወራውና አሁን የምናወራው ተለውጧል፡፡ በፊት እኮ…“ስማ ያቺ የኮተቤዋን፣ ያቺ እንኳን የቀበሌ ድንኳን በሚያክለው ቀሚሷ ስር ሁለት ሱሪ ትለብስ የነበረችው… አይተኸት ታውቃለህ!” ሲባል… “የእኔ ጌታ የሆነ ባለጊዜ ጠብ አድርጋ አሁን በአጠገቧ እንኳን አታልፍም አሉ…” አይነት የጋራ አጀንዳ ነበር።
ደግሞላችሁ… ገርልዬዋን የእንትን ሰፈር ልጆች ለክፈዋት ስለተካሄደው ክትክት…አንድ ትሪ ድንች ለሦስት ተበልቶ ስለማይጠገብበት…“አንድ በራድ” ሲባል የቀዘቀዘ ሻይ ስላቀረበው አስተናጋጅ… አንድ ብር ይዞ ባሻ ወልዴ ችሎት ብቅ ብሎ “ሀምሳ ሳንቲም ጨምር…” ተብሎ ሲሮጥ ስለመጣው ጩኒ… መአት የሚወራ ነገር ነበር፡፡
ዘንድሮ ግን ድሮ ምናምን ቀርቶ ከአሥራ እምስት ዓመት በኋላ ስትገናኙ የመጀመሪያው ዓረፍተ ነገር “አሁን ይቺ አገር ነች!” ምናምን አይነት ብሶት ነው። ምን አለፋችሁ…በቅጡ እንኳን የወዳጅነት ሰላምታ ሳንለዋወጥ… “ስማ በሻይ ጠቅሰን የምንበላው ዳቦ እንኳን እንዲህ ይወደድ!” እንባባላለን፡፡
እግረ መንገዴን የሆነች ያነበብኳት ነገር ትዝ አለችኝማ…
እሱና እሷ ተጋብተው የሠርጉ ስነ ስርአት ካለፈ በኋላ ሚስት አንድ መለስተኛ ሳጥን አልጋዋ አጠገብ ታስቀምጣለች፡፡ ለባሏም በምንም አይነት ሳጥኑን እንዳይከፍት ታስጠነቅቀዋለች፡፡ አርባ ዓመታት አለፉ፡፡ አንድ ቀንም አቶ ባል ነገሩ ይከነክነውና ሚስቱ ሳታውቅ ሳጥኑን ይከፍተዋል፡፡ ውስጡም ሦስት ባዶ የቢራ ጠርሙሶችና አንድ መቶ አርባ ሺህ ዶላር ያገኛል፡፡ ማታም ባል ሚስቱን “የእኔ ውድ አዝናለሁ ግን ሳጥኑን ከፍቼ ነበር፡፡ ሦስቱ ባዶ የቢራ ጠርሙሶች ምንድናቸው?” ይላታል። ሚስትም…
“ከሌላ ወንድ ጋር በተኛሁ ቁጥር አንድ ቢራ እጨልጥና ባዶውን ጠርሙስ ሳጥኑ ውስጥ አስቀምጠዋለሁ፣” ትለዋለች፡፡
ባልየውም ትንሽ ያስብና ‘በአርባ ዓመት ሦስት ጊዜ ብቻ መማገጥ ምንም አይደለም’ ብሎ ራሱን ያሳምናል፡፡ ቀጥሎም…
“እሺ፣ የጠርሙሶቹስ ይሁን፡፡ አንድ መቶ አርባ ሺህ ዶላሩን ምን ስትይ አጠራቀምሽው?” ይላታል፡፡ ሚስት ምን ብትለው ጥሩ ነው…
“ሳጥኑ ሦስት ጠርሙስ ይዞ ተጨማሪ ጠርሙስ አላስገባ ሲለኝ ባዶ ጠርሙሶችን በገንዘብ እየለወጥኩ ያስቀመጥኩት ነው…” ብላው አረፈች፡፡
ሰውየው የተዋሰውን የጓደኛውን መኪና ያጋጫል፡፡ ማታ ቤት ሲገባ ሚስቱ…
“መኪናው መገጨቱን ጓደኛህ ሲያይ ምን አለህ?” ትለዋለች፡፡
“ስድብ ስድቡን ትቼ ሌላውን ብቻ ልንገርሽ?”
“አዎ፣ ስድቡን ተወውና ሌላውን ንገረኝ፡፡”
“እንግዲያው ምንም ነገር አላለም፡፡”
ዘንድሮም ‘ስድብ፣ ስድቡን’ ስናወጣ ባዶ የሚሆኑ ንግግሮች፣ መግለጫዎች፣ ማብራሪያዎች መአት ናቸው፡፡
እናላችሁ… “ጓደኛ አታሳጣኝ…” ማለት ዘንድሮ ነው፡፡
እውነተኛ የልብ ጓደኞችን ያብዛላችሁማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Published in ባህል

ፎከር - 50 ለመጨረሻ ጊዜ የተመረተው ከ20 ዓመት በፊት ነው

   በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች፤ ከ50 ሰው በላይ እንዳያጓጉዙ የተጣለባቸው ገደብ ሊያሰራቸው እንዳልቻለ ጠቁመው ገደቡ እንዲነሳላቸው ጠየቁ፡፡  
የበረራ አገልግሎት ሰጪዎቹ፤ ከዚህ ቀደም የወንበር ገደቡን ጨምሮ የጋራዥ ቦታና ሌሎች በዘርፉ የሚታዩ ችግሮች ለስራቸው መሰናክል እንደሆኑባቸው ሲገልፁ ቆይተዋል፡፡
የናሽናል ኤርዌይስ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ ካፒቴን አበራ ለሚ ለአዲስ አድማስ  እንደተናገሩት፤ በአሁኑ ወቅት ከ79 ሰው በታች የሚጭን አውሮፕላን ገበያ ላይ የለም፡፡ በተለምዶ ፎከር - 50 በሚል የሚጠሩትና 50 ሰዎችን የሚጭኑት አውሮፕላኖች ለመጨረሻ ጊዜ የተመረቱት ከ20 ዓመታት በፊት ነው፡፡
“79 ሰው የሚጭነውን አውሮፕላን ገዝቶ 50 ሰው መጫን ኪሳራ ነው” ያሉት ካፒቴኑ፤ የወንበር ገደቡ ሊያሰራን ስላልቻለ ሊነሳ የሚችልበት መንገድ ቢኖር የግል የአቬሽን ዘርፍን ወደ አንድ ደረጃ ያሳድገዋል ብለዋል፡፡
በቅርቡ ኢትዮጵያ የዓለም ምርጥ የቱሪዝም መዳረሻ ተብላ መመረጧን ያስታወሱት ካፒቴን አበራ፤ በወንበር ገደቡ ምክንያት ወደ ሃገሪቱ በብዛት እየጐረፉ ያሉትን ቱሪስቶች ለማስተናገድ እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡ ገደቡ እንዲነሳ በተደጋጋሚ ጥያቄ ማቅረባቸውን አስታውሰውም፣ ይነሳል እየተባለ ሶስት ዓመታት ያለ ውጤት ማለፉን ገልፀዋል፡፡
ከወንበር ገደቡ በተጨማሪም በቦታ ችግር የተነሳ፣ የሰው ሃይሉ እያለ አውሮፕላን የሚያሰሩት ደቡብ አፍሪካ ድረስ በመሄድ መሆኑን ጠቁመው፤ ይሄም ነዳጅን ጨምሮ ለተለያዩ ወጪዎች እየዳረጋቸው እንደሆነ ካፒቴኑ ገልፀዋል፡፡
በአቬሽን ዘርፍ ለረዥም ዓመታት ያገለገሉት አቶ ስንታየሁ በቀለ በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅት በየትኛውም አገር የወንበር ገደብ እንደሌለ ገልፀው፣ የገደቡ መነሳት ለአገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ እያደገች ያለች አገር በመሆኗ የኢኮኖሚ እድገቷን ተከትሎ የቱሪስት ፍሰቱም ስለሚጨምር ቱሪስት የማስተናገድ አቅሟን ልትጨምር እንደሚገባ አቶ ስንታየሁ ያስረዳሉ፡፡ ኢትዮጵያ በአቬሽን ኢንዱስትሪው መልካም ስም ከተቀዳጁ አገራት መካከል አንዷ በመሆኗ በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ፈትቶ፣ የግሉን ዘርፍ በመደገፍ የአቬሽን ዘርፉን ማሳደግ እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡
የወንበር ገደብ መነሳቱ የተሻሉ አውሮፕላኖችን ለማስገባት እድል ስለሚፈጥር ቱሪስቶች ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላቸዋል ያሉት አቶ ስንታየሁ፤ ቱሪስቶቹ በትናንሽ /ቻርተር/  አውሮፕላኖች የሚጠየቁት ከፍተኛ ክፍያም እንደሚቀንስላቸው አብራርተዋል፡፡

Published in ዜና

 ኢህአዴግ፤ “ኒዮሊበራል” በማለት አሜሪካን መዝለፍ ያዘወትራል። ታዲያ እንዴት፣ ኦባማ “ድንገት”
ተነስተው ዋና የኢህአዴግ አድናቂ ይሆናሉ? (ድንገተኛ አይደለም፡፡ አባማ ነባር ሃሳባቸውን ላለፉት
6 ዓመታት በተደጋጋሚ ሲገልፁ ቆይተዋል፡፡)
· የዲያስፖራ ፖለቲከኞች፤ ለኦባማ የምርጫ ዘመቻ ቀስቅሰዋል። ዛሬ ግን፣ የኦባማ ጉብኝት ድንገተኛ
ክህደት ሆኖባቸው የተቃውሞ ሰልፍ ያካሂዳሉ። (ክህደት አይደለም፡፡ ኦባማ, የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸውን
አልቀየሩም)።
· “ኦባማ ቢያሸንፉ፤ኢህአዴግ ደስታውን አይችለውም” (ጥቅምት 8 ቀን 2001 ዓ.ም በአዲስ አድማስ
የወጣ ትንታኔ። የኦባማ የሃሳብ ቅኝት ለኢህአዴግ እንደሚመች የሚተነትን ጽሑፍ ነው፡፡)


የዘንድሮ ፖለቲካ፣ ብዙዎች ከሚገምቱት ውጭ፣... በግራ በኩል ሲጠብቁት በቀኝ በኩል የሚነጉደው ለምንድነው? “ግራ መጋባት” ይሉሃል ይሄ ነው። እንዲህ የምንሆነው፣ ሳናስተውል ስለቀረን ወይም ሚዛን ስለጠፋብን ይሆን? እንደዚያ ከሆነ፣ ጥፋቱ የኛ ነው።
ግን፣  ሌላውስ ዓለም መች ከግራ መጋባት ዳነ! “ለየትኛውም አገር ቢሆን፣ የዘመኑ ፖለቲካ መላ የለውም’ኮ” ሊባል ይችላል። በእርግጥም፣ ብዙ ሰዎች ከሚጠብቁት ውጭ፣ ዓለማችን ከዳር ዳር እየተናጠች ነው። ግራ መጋባት የተበራከተው፣ በኢትዮጵያውያን ላይ ብቻ አይደለም። ቢሆንም ግን፣ ኢትዮጵያ ላይ በዛ፣ ተደጋገመ፣ ተደራረበ።
በተለይ በተለይ፣ ኢትዮጵያን በሚመለከት፣ የፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ አቋምና ጉብኝት በፍፁም ድንገተኛ ሊሆንብን አይገባም፡፡ ከስድስት ዓመት በላይ ካላንቀላፋን በስተቀር፣ የኦባማ አስተሳሰብና አዝማሚያ ገና ድሮ ፍንትው ብሎ ሊታየን ይገባ ነበር። ለምን?
አንደኛ ነገር፣  የትርምስ ዘመን ላይ ነን፡፡
“በአረቦች አብዮት” ሳቢያ፣ በርካታ አገራት ከድጡ ወደ ማጡ ተሸጋግረው ማብቂያ ወዳልተገኘለት ትርምስ መግባታቸው፣ ለአሜሪካ ብቻ ሳይሆን ለአውሮፓም አሳሳቢ ሆኗል። “የፖለቲካ ለውጥ መጣ” ማለት፣ “መልካም ለውጥ መጣ” ማለት ላይሆን እንደሚችል አይተዋላ።
አሳዛኙ ነገር፣ የዘመኑን ትርምስ በማየት የተሳሳተ ድምዳሜ መያዛቸው ነው፡፡ እናም፤ “በአለም ዙሪያ የግለሰብ ነፃነትን፣ የፖለቲካ ምርጫዎችንና የነፃ ገበያ አሰራርን የሚያስፋፋ የፖለቲካ ለውጥ ለማምጣት፣ ተፅእኖ ማድረግ ዋጋ የለውም። እንዲያውም ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል” ወደሚል አስተሳሰብ አዘንብለዋል - አውሮፓና አሜሪካ። “በአፍሪካና በአረብ አገራት... በተለይም ደግሞ፣ እንደ አፍሪካ ቀንድ በመሳሰሉ የውጥረት አገራት ውስጥ፣ የተረጋጋ መንግስትና የኢኮኖሚ እድገት ከተገኘ በቂ ነው” ወደሚል ተስፋ ቢስነት እየወረዱ ነው።
አውሮፓና አሜሪካ፣ በኢትዮጵያ ለሚካሄድ የፖለቲካ ምርጫ ሲሰጡት የነበረ ትኩረት ምን ያህል እንደቀነሰ በዘንድሮው ምርጫ በግልፅ ታይቶ የለ!!
የኢትዮጵያ መንግስት፣ በተረጋጋ ሁኔታ የኢኮኖሚ እድገት እስካስመዘገበ ድረስ፣ ለአካባቢው አገራት መረጋጋት እስካገዘ ድረስ፣ ከአውሮፓና ከአሜሪካ የወዳጅነት እርዳታ ማግኘቱ የማይቀር ነገር ነው - በዛሬ አለማቀፍ የትርምስና የሽብር ዘመን።
ይህንን ማስተዋልና ማገናዘብ ከቻልን፣ የኦባማ ጉብኝት በጭራሽ ድንገተኛ ተዓምር ወይም ዱብዳ አይሆንብንም፡፡
ሁለተኛ ነገር፡-
ባራክ ኦባማ፣ ለኢትዮጵያ መንግስት የሚያሳዩት የወዳጅነት አቋም ግን፣ ከዚህም ያለፈ፣ ከዚህም የቀደመ ነው። ገና ሳይመረጡ በፊት የያዙት አቋም ነው።
“የአሜሪካ እጅ ረዝሟል፤ ማሳጠር አለብን” ብለው የሚያምኑት ባራክ ኦባማ፤ አሜሪካ በየአገሩ ጣልቃ ገብታ “የግለሰብ መብት አክብሩ፤ የፖለቲካ ምርጫ አካሂዱ፤ የነፃ ገበያ አሰራር አስፋፉ” እያለች ተፅእኖ ማሳረፍ እንደሌለባት ደጋግመው ተናግረዋል። ይሄ፣ ከዋና ዋና የኦባማ መርሆች መካከል አንዱ ነው። ሳይመረጡ በፊትም ሲናገሩት የነበረ፣ ከተመረጡ በኋላም በተግባር የገፉበት የውጭ ግንኙነት መርህ ነው።
(አብዛኛው ኢትዮጵያዊ አሜሪካን በጥሩ አይን የሚያይ ቢሆንም፤ ለአሜሪካ በጎ አመለካከት የሌላቸውና አሜሪካን ማብጠልጠል እንደ አዋቂነት የሚቆጥሩ ብዙዎቹ የአገራችን ፖለቲከኞች፣ የኢህአዴግና የተቃዋሚዎችም ጭምር፣ እንዲሁም ምሁራንና ጋዜጠኞች... በአብዛኛው በዚህ የኦባማ አስተሳሰብ እንደሚስማሙ እገምታለሁ)።
“ከሁሉም ከሁሉም በፊት፣ የኢኮኖሚ ጉዳይ ይቀድማል”... ማለትም በቁንፅሉ... ምግብ፣ መጠለያ፣ የስራ እድል የማሟላት ጥያቄ ይቀድማል ባይ ናቸው ኦባማ። እዚህ ላይ የአሜሪካ ድርሻ፣ “የግለሰብ መብት፣ የፖለቲካ ምርጫና ነፃ ገበያ” የሚሉ ቅድመ ሁኔታዎችን ትታ፣ እርዳታ መስጠት ብቻ ይሆናል። ኦባማ ይህንን በተደጋጋሚ ተናግረዋል፤ በተግባርም እየሰሩበት ይሄውና ስድስት አመታት ተቆጥረዋል።
ታዲያ፣ ይህንን ሁሉ ሰምተንና አይተን፣ ባራክ ኦባማ በኢትዮጵያ ላይ ምን አይነት አቋም እንደሚከተሉ መገመት ያቅተናል? ቢያንስ ቢያንስ፣ ፖለቲካን እንጀራቸው ወይም ፖለቲካን ሙያቸው ያደረጉ ሰዎች፣ ይህንን መሳት አልነበረባቸውም።
ግን ስተውታል፤ በረዥም ርቀት ስተውታል። በቃ፣ የባራክ ኦባማ አቋምና የኢትዮጵያ ጉብኝት፣ ለአገራችን ፖለቲከኞች ግራ የሚያጋባ ድንገተኛ ተዓምር ወይም ዱብዳ ሆኖባቸዋል።
በአንድ በኩል፣ ኢህአዴግ፣ በተለመደው የሶሻሊስቶች ፈሊጥ “ኒዮሊበራል” እያለ ከሚያጣጥላት አገር... ካልጠበቀው አቅጣጫ... ከአሜሪካ፣ ለዚያውም ዝነኛው ባራክ ኦባማን የመሰለ አድናቂ ማግኘቱ ያስገርመዋል።  
ተቃዋሚዎችስ?
ያኔ በ2001 ዓ.ም፣ “ባራክ ኦባማ ከተመረጡ፣ በኢህአዴግ ላይ ጫና በማሳረፍ የፖለቲካ ለውጥ እንዲመጣ ይረዱናል” በማለት፣ ኮሚቴ አቋቋመው ቅስቀሳ ሲያካሂዱ የነበሩ የዲያስፖራ ፖለቲከኞችስ? በነሱ ቅስቀሳ ባይሆንም፣ ኦባማ ተመርጠው በፕሬዚዳንትነት ሲሰሩ ስድስት ዓመታት ተቆጥረዋል። ይሄን ሁሉ አመት የኦባማን አስተሳሰብና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሳይገነዘቡ የቆዩ የአገራችን የዲያስፖራ ፖለቲከኞች፣ በኦባማ አቋም ተበሳጭተው ለተቃውሞ ሰልፍ የወጡት አሁን ነው - የኦባማ ጉብኝት፣ ድንገተኛ ክህደት ሆኖባቸው።
ላለፉት ስድስት አመታት፣ ኢህአዴግና ተቃዋሚዎች፣ የባራክ ኦባማን የውጭ ፖሊሲ ለማወቅ ትንሽ ጥረት ቢያደርጉ ኖሮ፣ ይሄ ሁሉ ግራ መጋባት ባልተፈጠረ ነበር። ለኢህአዴግ፣ ድንገተኛ አድናቆት አይሆንበትም ነበር። ለዳያስፖራ ተቃዋሚዎችም፣ የኦባማ ጉብኝት ድንገተኛ ክህደት ሆኖ ባልታያቸው!
ኢህአዴግና የዲያስፖራ ተቃዋሚዎች ለአመታት ያህል እንዲህ ግራ የተጋቡት ለምንድነው?
በእርግጥ፣ ነገሩ ከተፈፀመ በኋላ፤ የጉብኝት ዜናው ከዳርዳር ከተወራ በኋላ… “ነገሩን መሳት አልነበረባችሁም፣ ኦባማ ለኢህአዴግ እንደሚመቹ ማወቅ ነበረባችሁ፤ መገመት ነበረባችሁ” ብሎ መናገር ቀላል ነው። ነገር ግን፣ ዛሬ ሳይሆን ከስድስት ዓመት በፊት በአዲስ አድማስ የወጡ ሁለት ፅሁፎችን ማስታወስ ይቻላል።
አንደኛው ፅሁፍ፣ ነሐሴ 3 ቀን 2000 ዓ.ም፡፡
“ባራክ ኦባማ ለኛ ምናችን ናቸው?” በሚል ርዕስ የወጣ ፅሁፍ ነው። ባራክ ኦባማ፣ በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች የአፍሪካ መንግስታት ላይ የፖለቲካ ጫና ለማሳደር እንደማይፈልጉ ከነምክንያቱ ይተነትናል ፅሁፉ። እንዴት? ከርዕሱ ስር፣ የፅሁፉን ይዘት የሚገልፁ ዋና ዋና ነጥቦች በጉልህ ተዘርዝረዋል።
ባራክ ኦባማ፣ “ዲሞክራሲና ሰብአዊ መብት በአለም እንዲስፋፋ አደርጋለሁ አላሉም” ይላል አንዱ ነጥብ።
ሌሎቹንም ነጥቦች ልጥቀስላችሁ፡-
ባራክ ኦማባ … “ለድሃ አገራት የኢኮኖሚ እርዳታ በእጥፍ እጨምራለሁ ብለዋል፤ የምርጫ ውድድርን በመተግበር አገራትን አሻሽላለሁ አላሉም፡፡”
ባራክ ኦባማ … “ትምህርትና ጤና በማስፋፋት በአለም ለውጥ ይመጣል ብለዋል፤ በድሃ አገራት የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ መጠናከር ይገባዋል አላሉም፡፡”
እነዚህን የባራክ ኦባማ መርሆች በማገናዘብ ነው፤ በኢትዮጵያ ላይ ምን አይነት አቋም እንደሚኖራቸው በፅሁፉ የተተነተነው።
ሁለተኛው ጽሑፍ ጥቅምት 8 ቀን 2001 ዓ.ም።
በአዲስ አድማስ የወጣው ይሄኛው ፅሁፍም ተመሳሳይ ትንታኔ ያቀርባል። ርዕሱ እንዲህ ይላል፡
“ኦባማ ቢያሸንፉ፤ ኢህአዴግ ደስታውን አይችለውም”
ኦባማ ቢመረጡ፣ “የአፍሪካ መንግስታት፣ የኢትዮጵያ መንግስትም ጭምር ከአሜሪካ የፖለቲካ ተፅእኖ ይገላገላሉ፡፡ በዚያ ላይ ተጨማሪ የገንዘብ እርዳታ ያስገኝላቸዋል” የሚል ይዘት አለው ፅሁፉ።
(“ኦባማ ቢያሸንፉ፤ ኢህአዴግ ደስታውን አይችለውም” የሚለው ፅሁፍ፣ ኦባማ ለኢህአዴግ እንደሚመቹ የሚገልፅ በመሆኑ ትክክለኛ ትንታኔ ነው። ነገር ግን፣ ስህተትም አለው። ኢህአዴግ ነገሩን አገናዝቦ፣ በኦባማ መመረጥ ይደሰታል ብሎ መተንበዩ ስህተት ነው። ኢህአዴግ ነገሩን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አልተገነዘበውማ። ተቃዋሚዎችም እንዲሁ።)    
ለማንኛውም፣ እነዚህን ፅሁፎች ለመጥቀስ የፈለግሁት ለምንድነው? የአገራችን ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች ተጨባጭ መረጃን በማገናዘብ፣ ያኔ ድሮ የኦባማ አስተሳሰብንና አዝማሚያን ማወቅ ይችሉ እንደነበር ለማሳየት ነው የፈለግኩት። ለማወቅ ያልቻሉት፣ ነገሩ ከባድ ስለሆነ አይደለም። በጭፍን ስሜት የመነዳት ልማድ ነው እንዲህ ለስህተት የሚዳርጋቸው።

• ስጋት ከተጋረጠባቸው 14 ሀገራት ውስጥ ተካታለች
• ሴኔጋል፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ፣ሞዛምቢክ በዕዳ ተዘፍቀዋል

      የውጪ ብድር እዳ ኢኮኖሚያቸውን ሊፈታተን ይችላል የሚል ስጋት ከተጋረጠባቸው 14 የአለም
አገራት ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን ዘ ጋርዲያን የአለም ባንክን ሪፖርት ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ በአሁን ወቅት ኢትዮጵያ ከፍተኛ የብድር እዳ እንዳለባት የጠቀሰው ሪፖርቱ፤ ከአጠቃላይ አገራዊ ምርቷ 45 በመቶ የሚሆነው ከብድር የተገኘ ገንዘብ እንደሆነ ጠቁሞ፤ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ይህ አኃዝ ወደ 65 በመቶ ሊያሻቅብ እንደሚችል ጠቁሟል፡፡ ከለጋሽ ተቋማትና ሃገራት የሚገኝ ብድር ለአጠቃላይ አገራዊ ምርት ያለው አስተዋጽኦ ከ30 በመቶ በላይ ከሆነ ሀገራት ወደ ከፍተኛ የእዳ ቀውስ እያመሩ መሆኑን እንደሚያመለክት የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ኢትዮጵያም በዚህ የአደጋ ቀጠና በከፍተኛ ደረጃ ከገቡ 14 የአለም  ሀገሮች መካከል ተጠቅሣለች።  ከፍተኛ የውጭ እዳ ውስጥ ተዘፍቀዋል የተባሉት 14 ሀገራት ኢትዮጵያን ጨምሮ ቡታን፣ ኬፕ ቨርዲ፣ ዶሚኒካ፣ ጋና፣ ላኦስ፣ ሞሪታኒያ፣ ሞንጐሊያ፣ ሞዛምቢክ፣ ሣሞኣ፣ ሣኦቶሜ ፕሪንቼቤ፣ ሴኔጋል፣ ታንዛኒያ እና ኡጋንዳ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል 24 የአለም ሀገሮች የውጭ እዳቸው በሚያሰጋ ደረጃ እየጨመረና ወደ አደጋው ቀጠናም እየተንደረደሩ ነው በሚል ተጠቅሰዋል፡፡
አንዳንድ በአስጊ ደረጃ እዳ ውስጥ ተዘፍቀዋል የተባሉ ሀገራት፣ የተበደሩትን ገንዘብ ለተገቢው
አላማ መጠቀም አለመቻላቸው ለቀውስ እንደዳረጋቸው በሪፖርቱ የተጠቆመ ሲሆን በዚህ ረገድ ጋና ምሣሌነት ተጠቅሳለች፡፡ ሌሎችም አዋጭ የሆነ የብድር አመላለስ ስርአት ባለመከተላቸው የችግሩ ሠለባ እየሆኑ እንደመጡ የጠቆመው ሪፖርቱ፤ እነዚህ ሀገራት ከዚህ እዳ የሚወጡበትን መንገድ ካላጤኑ ከፍተኛ ቀውስ ሊገጥማቸው ይችላል ብሏል፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ የግል ኩባንያዎችና መንግስታት አለም ባንክን ከመሳሰሉ አበዳሪ ተቋማት ከ2009 እ.ኤ.አ ጀምሮ በየአመቱ የሚበደሩት ገንዘብ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ነው ተብሏል፡፡ በ2013 እ.ኤ.አ የአለም ሀገራት አጠቃላይ የብድር መጠን 11.3 ትሪሊዮን ዶላር ሲሆን በ2014 13.8 እንዲሁም በዘንድሮው አመት 14.7 ትሪሊዮን ዶላር መሆኑን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ 

Published in ዜና

ዛፍ አይቆርጥም አሉ!፤ እግዚሄር ሲቆጣ፤
“Selfless” ያልነው ሰው፥ ሰልፍ… ይዞ መጣ።

ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ እድሜውንና የእውቀት ደረጃውን በማይመጥን ሁኔታ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ፣ በቁም ነገር መፅሔት፣ እና በመሳሰሉት ሚዲያዎች ላይ ተገቢ ባልሆነ መንገድ ጥላሸት ሊቀባኝ ሞክሯል፤ እንግዲህ እርሱ እንደፈለገ እንዲናገር ሌላው ደግሞ ዝም እንዲል የሚፈቅድ ዓለማዊ ይሁን ኃይማኖታዊ፤ ሞራላዊ ይሁን ህጋዊ ማቀፍ የለምና፤  ተገቢ በሆነ ሁኔታ የጉዳዩን ትክክለኛ ገፅታ በማሳየት እውነቱን አስረዳለሁ።ከሁሉም በላይ የሚገርመው ነገር ደግሞ በዚህ መሰረተ ቢስ ውንጀላው ላይ “አስራትና ጓደኞቹ፣
አስራትና ሌሎች ተማሪዎቼ” እያለ የሌሎቹን በድፍኑ ሲያልፈው፣ የእኔን ስም ግን ከሃያ ጊዜ በላይ ማንሳቱ ነው። እሱ እንደሚለው ከዚህ መፅሐፍ ጀርባ ሊኖሩ ይችላሉ ብሎ ያሰባቸው ሌሎች ሰዎች በስማቸው ያልጠቀሰበት የራሱ የሆነ ምክንያት ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ፡፡ አንድም እኔ ላይ የሚለውን ያህል የሌሎች ስም ቢጠቅስ የሚመለስለትን የአፀፋ መልስ ስለሚያውቅ ሊሆን ይችላል፤ አንድም ደግሞ እኔ በሚዲያው አካባቢ አዲስ ሰው ስላልሆንኩ፣ የእኔን ስም ደጋግሞ ሲያነሳ እኔን የጎዳ መስሎት ሊሆን ይችላል፤ ወይም የእሱን ስም ባጠፋ ማንም ምንም አይለኝም፤ የሚቆረቆርለት ወገን የሌለው፤ ከመንግስትም የተጣላ፤ ብቻውን የሆነ ሰው ነው ብሎ አስቦ ሊሆን ይችላል፤ ለእኔ ከፍትሀዊነትና ከሰብዕና መውደቅ ማለት ይሄ ነው።
ለመሆኑ ከመሀመድ ሀሰን ጀርባ አሉ የሚላቸው ሰዎች ስንት ናቸው?! ለምሳሌ “አስራት ጓደኞቹ ወይም አስራትና ሌሎች ተማሪዎቼ” ሲል ከተማሪዎቹ ስንቶቹን ነው በዚህ ስራ ላይ እየወነጀላቸው ያለው?! ለእኔ በጣም የሚገርም ነገር ነው። “በዙሪያዬ ያለው ሰው ሁሉ ከጀርባ ያሴርብኛል” ዓይነት አስተሳሰብ የሆነ ህመም ምልክት ነው የሚመስለኝ ለመሆኑ ይሄ የመሀመድ ሀሰን መፅሀፍ ምን ተአምር ስለያዘ ነው ይሄ ሁሉ ሰው ከጀርባ ሊሰፍለት የሚችለው?! ለእኔ እንቆቅልሽ የሆነብኝ ነገር ይሄ ነው። እሱ እንግዲህ ከገንዘብ ማጋበስ ጋር ነው ሊያያይዘው የሚሞክረው፤ ነገር ግን እሱ እንደሚለው ብዙ ሰዎች ከዚህ ጀርባ ካሉ ነገሩ ገንዘብ ፍለጋ ብቻ ይሆናል የሚያስብል አይደለም፤ ለምሳሌ ከዚህ መፅሐፍ ምን ያህል ጥቅም ነው ሊገኝ የሚችለው?! የሚለውን ማየት ይቻላል፤ ዶ/ር ዳኛቸው ከመፅሐፍ ሽያጭ ገንዘብ ማጋበስ የሚቻል ከመሰለው ምናልባት እስካሁን መፅሐፍ አሳትሞ ስለማያውቅ ሊሆን ይችላል፤ ቢያንስ ግን ከወረቀት መወደድ ጋር ተያይዞ የማተሚያ ቤት ወጪው በአጠቃላይ ከመፅሐፍ ህትመት የሚገኘው ጥቅም ያን ያህል የማዩጓጓ አለመሆኑን መረዳት መቻል ነበረበት! ለምሳሌ እኔ አራት መፅሐፍ አሳትሜያለሁ፤ አንዳንዶቹ እስከ አምስት ጊዜ ታትመዋል፡፡ ለምሳሌ “ከሀገር በስተጀርባ” አምስት ጊዜ ነው የታተመው፣ “ጎበዝ ተማሪ የመሆን ሚስጥር” ሶስት ጊዜ ታትሟል፤ “መለስ እና ግብፅ” ሁለት ጊዜ ታትሟል፤ ነገር ግን ከዚህ ሁሉ ያገኘሁት ነገር በጣም ትንሽ ነው። የእለት ጉርስ ከመሸፈን ውጪ የተረፈኝ ነገር የለም፤ ከዚህ መረዳት የሚቻለው የመሀመድ ሀሰን መፅሐፍ ከጀርባ አሉበት እየተባሉ ያሉት ሰዎች ለገንዘብ ብለው ነው የሚለው
አነጋገር አሳማኝ አይደለም፤ እውነት እንዲመስል ሴራውን ከፍ ማድረግ ነበረበት፤ አለበዚያ ውንጀላው ውሀ የሚያነሳ አይሆንም። እኔ መፅሐፉን ማከፋፈሌ ዳኛቸው ከሚለው ነገር ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም፤ መፅሐፉ ችግር ካለው ከፀሐፊው ጋር ነው መጨረስ ያለበት፡፡ እርሱ አልፈልገውም፤ እኔ እምፈልገው ሌሎች ነው ካለ ደግሞ ይሄ ከመፅሐፉ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም። በአጠቃላይ የሚለው ሁሉ ከምክንያት የወጣ ነገር ነው፤ በዚህ አካሄድ ከሆነ መፅሐፉን የሚሸጡት መፃህፍት መደብሮችና አዟሪዎችም፣ ገዝተው ያነበቡትም ሁሉ መጠየቅ ሊኖርባቸው ነው ማለት ነው። እንግዲህ እንዲህ ዓይነቱ ህግ እስካሁን በዓለም ላይ የለም።ከዩኒቨርሲቲው ጋር ያለውን ፀብ ወደ እኛ ወደ ተማሪዎቹ ለማዞር የሄደበት መንገድ ስህተት ያለበት ነው፤ አህያውን ፈርቶ ዳውላውን ይላል ሀበሻ ሲተርት፤ ይሄም እንደዚያ ዓይነት ነው። ተማሪዎቼ አማካሪ ለምን ተቀየረላቸው ብሎ ከሆነ የተናደደው፤ እሱ ሌላ ነገር ነው፤ የሚያማክራቸው
ተማሪዎች ተመርቀው ስራ መያዝና ቤተሰባቸው መርዳት ስላለባቸው በእርሱ ምክንያት ቢጉላሉ
ተገቢ አይሆንም፤ ሲሆን ሲሆን የተሰጠውን ሀላፊነት መከታተል የነበረበት ራሱ ነው፡፡ ከስራ ሲታገድ ከእኔ ጋር ያሉት ተማሪዎች እንዴት ነው የሚሆኑት ብሎ ዲፓርትመንቱን መጠየቅ ነበረበት፤ እኔም በጊዜ ሊያሰናብተኝ ይገባ ነበር፤ በአስራ አንደኛው ሰዓት ስልክ ደውሎ አማካሪው አልሆንም ካለ በኋላ፤ መልሶ እኔኑ አልነገረኝም ብሎ ይወነጅለኛል፤ እኔ መረጃው ቢኖረኝማ ጨርሼ እመረቅ አልነበር! “ስለመፅሐፉ አልነገረኝም፤ መታገዱንም አልነገረኝም” ሲል ወሬ እንዳመላልስለት የቀጠረኝ እኮ ነው የሚመስለው።
 የገረመኝ ደግሞ በዚህ መፅሐፍ ላይ እጃቸው ያለበት ሰዎች አማካሪያቸው ብሆን ኖሮ አሳያቸው ነበር ዓይነት ንግግሩ ነው፤ ሲኮንነው የኖረው አንድ ሰው ያለውን ስልጣን ተጠቅሞ ሰው ላይ ጉዳት የማድረስ ወንጀል ራሱም እንደሚፈፅመው የሚያሳይ ነው፡፡ በአጠቃላይ እያነሳው ያለው ሀሳብ አሉሽ አሉሽ ላይ የተመሰረተ፤ የሰፈር ባልቴቶች ፀብ ነው የሚመስለው፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ ከምክንያታዊነትና ከምሁራዊነት አውጥቶ ተራ ወደ ሆነ አሉባልታ ስላወረደው ነው። በመሰረቱ የዶ/ር ዳኛቸው ፅሁፍ “እንዲህ እንትና ነገረኝ፤ እንትና እንዲህ አለኝ” ከሚል ውጪ አንድም የረባ የመከራከሪያ ነጥብ አላየሁበትም። የፈረንሳዩ ፈላስፋ ሬኔ ዴካርት እኮ የምናደንቀው የራሱን ሀሳብ ሳይቀር ትክክል ላይሆን ይችላል ብሎ ሀሳቦቹን ሁሉ ለመመርመር የተነሳ ሰው በመሆኑ ነው። እንዴት ይህን ፍልስፍና ሲያስተምርን የኖረን ሰው፣ ሰዎች የሚነግሩትን ሁሉ ሳይጠራጠር እንዳለ ተቀብሎ ያስተጋባል። አሁን ሆኜ ሳየው ይሄ መፅሐፍ ለዶ/ር ዳኛቸው ጥሩ ነገር ይዞለት የመጣ አይመስለኝም፤ ራሱን እንዲያዋርድ፤ ውስጣዊ ማንነቱ እንዲታይ በር የከፈተለት ይመስላል፡፡ ይሄ የሆነው ደግሞ ገንዘብ ስላጓጓው ይመስለኛል። መሀመድ ሀሰን እኮ ከእሱ ተሽሎ ተገኘ፤ ከመፅሐፉ ምንም አልፈልግም፤ ተሽጦ የሚገኘውን ትርፍ ሁሉ ላንተ ልስጥህ ብሎታል፤ እንግዲህ ይሄ ልጅ ምን እንዲያደርግለት ነው የሚፈልገው።ዶ/ር ዳኛቸው ለበድሉ የሰጠሁትን ተገቢ መልስ ሲተች፤ “አስራትና ጓደኞቹ ዶ/ር በድሉን የመሰለ ራሱን በምሁራዊ ግብር ያስመስከረ ሰው እንደ እኩያቸው በመቁጠር መዘባበቻ አደረጉት በማለት ኮንኗል። እኔ የምለው ራሱን በምሁራዊ ግብር ያስመሰከረ ሰው ስህተት ሲፈፅም፣ የሰው ስም አንስቶ ሲዘረጥጥ ዝም መባል አለበት ወይ?! እንዲህ ያለን ሀሰታዊ የስም ማጥፋት ዘመቻ ሲፈፅምብህ፣ ራስህን ለመከላከልና እውነታውን ለማስረዳት የግድ በእርሱ ደረጃ መገኘት ያስፈልጋል ወይ?! ቁም ነገሩ ራስን በምሁራዊ ደረጃ ማስመስከርና አለማስመስከር አይደለም፤ ቁም ነገሩ የአቋም፤ የመርህ፣ የሞራልና የእምነት ነው። አንድ ሰው የሚለካው ከዚህ አንፃር ነው እንጂ ካለበት የትምህርት እርከን አይደለም፤ የተማረ ሆኖ አድርባይነት የሚያጠቃው ከሆነ፤ ውሸታም ከሆነ በምንም መንገድ የሚከበር የሚታፈር ሰው ሊሆን አይችልም። ሌላው “ከዶ/ር በድሉ ጋር በእኩልነት ደረጃ መነጋገራችን በዩኒቨርሲቲው የእውቀት ዕርከን እየተደፈጠጠ የመጣበትን ኹኔታ ማሳያ ነው” ይላል፤ ይህ የእውቀት እርከን የተባለው ሀሳብ በራሱ ስሑት አገላለፅ ይመስለኛል፤ የትምህርት ደረጃ እርከን ነው ሊኖር የሚችለው፤ ጠቅላላ እውቀትን በሚመለከት አንድ ወጥ የሆነ የሆነ፣ ሁሉንም ሰው በአንድ የሚያቅፍ የእውቀት ደረጃና እርከን ያለ አይመስለኝም፡፡ ዶ/ር በድሉ በተማረው ትምህርት ከእኔ የተሻለ እውቀት ሊኖረው ይችል ይሆናል፤ እኔ በተማርኩት ትምህርት ደግሞ ከእርሱ የተሻለ እውቀት ሊኖረኝ ይችላል። በፍፁም ሁለት ሰዎች እኩል ሊሆኑ አይችሉም፤ የተለያየ እውቀትና ችሎታ ነው የሚኖራቸው። በመሰረቱ ዶ/ር ዳኛቸው አስራትና ጓደኞቹ የሚለው ዶ/ር በድሉ በእኔ ላይ ለሰነዘረው ሀሰተኛ ውንጀላ መልስ የሰጡ ሰዎችን ነው፤ የበድሉ እኩዮች አይደላችሁም የሚላቸው እንግዲህ በበድሉ ፅሁፍ ላይ አስተያየት የሰጠነው እኔ፣ ሰለሞን ስዩም እና ይባቤ ነን። ከበድሉ ጋር የማይተናነስ ወይም የተሻለ ስራና ስም ያለን ሰዎች ነን። እንዲያውም እኔ ራሴን ከበድሉ ጋር እኩል አድርጌ  አላይም፤ እንደዚያ ቢሆንማ ባንድ ኮሌጅ ውስጥ ተራ ሌክቸረር ሆኜ እቀር ነበር። ሌላው የገረመኝ የእሱን ውንጀላ ደግፈው የጻፉትን እንደፍትሃዊያንና ለእውነት ጥብቅና እንደቆሙ አድርጎ ሲያቀርባቸው፤ ተገቢ ካልሆነ ውንጀላ ራሳቸውን የተከላከሉና በሚመስላቸው መንገድ በጉዳዩ ላይ ሀሳብ የሰጡትን ደግሞ እንደ ጥራዝ ነጠቅ አድርጎ ሲያቀርባቸው ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ የእኔ ጓደኞች እንደሆኑ አድርጎ አቅርቧቸዋል። እንዲህ ዓይነቱ በአንድ ጉዳይ ላይ የተለያየ መለኪያ
(Double Standard) መያዝ መቼም ከአንድ የፍልስፍና እውቀት አለው ተብሎ ከሚታሰብ ሰው
የሚጠበቅ አይደለም። ለምሳሌ ሰለሞን ስዩም በአንድ ወቅት ከዶ/ር በድሉ ጋር በጋዜጣ ስለተመላለሱበት ጉዳይ የጋዜጣውን ስምና የወጣበትን ቀን ጠቅሶ፤ የበድሉ አቋም ምን እንደነበረ ለማሳየት በአባሪ መልክ በመፅሐፉ ውስጥ በማከታቱ ነው ዶ/ር በድሉ ከእኔ ጋር አያይዞ የፃፈበት፤ “የእኔን ፅሁፍ ከራሱ ጋር ጠርዞ አሳተመ” ብሎ የወነጀለው። ለዚህ ተራ ውንጀላ ተገቢ መልስ ሰጥቶታል፤ “የሚኮረጅ ነገር የለህም” ነገሩን ጠቅለል አድርጌ ሳየው ዘመቻው በመፅሐፉም ሆነ በአማካሪነቱ ጉዳይ አይመስለኝም፤ ይሄ ሁሉ ሽፋን ነው፤ የሌላ የሶስተኛ አካል ረጅም እጅ ያለበት መስሎ ነው የሚሰማኝ። በዚህ ሀገር ምንም ተደብቆ የሚቀር ነገር ስለሌለ ጊዜው ሲደርስ እውነታው ፍርጥርጥ ብሎ ይወጣል፤ ይሄ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። ዛሬ ወዳጅ መስለው እያሳሳቱት ያሉት ሰዎች ነገ አጠገቡ እንደማይቆሙ የታወቀ ነው። እንግዲህ “ሰላም አስኗል፤ በዚህም ሊኮሩ ይገባል” ያላቸው ሰዎች (መቼም እሱ በሰላምና በፀጥታ መሀል ያለው ልዩነት ይጠፋዋል ብዬ አላስብም) አሁን ደግሞ ፍትህ አስፍኗል፤ እያለ ነውና ፍትህ ይስጡት፡፡ መሀመድ ሀሰንም ፍትህ ሲያጣ ያኔ እናያለን፡፡ መቼም ፍርድ ቤቱ የሁላችንም ነው፡፡




     የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ3ኛው ዓለም አቀፍ ፋይናንስ ለልማት ኮንፈረንስ ላይ ለመካፈል ለመጡ ንግዶች የአገር ውስጥ ጉብኝት ልዩ ፓኬጅ አዘጋጅቶ የቱሪስት መስህብ የሆኑ ስፍራዎችን እንዲጎበኙ እያደረገ ነው፡፡ አየር መንገዱ ፓኬጁን ያዘጋጀው ዩኔስኮ እውቅና ሰጥቷቸው በዓለም ቅርስነት የመዘገባቸውንና የአውሮፓ የቱሪዝምና ንግድ ም/ቤት ጠቅላላ ጉባኤ ኢትዮጵያን የ2015 የዓለም ምርጥ የባህላዊ ቱሪዝም መዳረሻ በማለት የመረጠበትን ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና ሰው ሰራሽ የቱሪስት መስህቦች ለኮንፈረንስ የመጡ እንግዶች እንዲጎበኙት በማድረግ ቱሪስቶችን ለመሳብና እንዲሁም ለአገር ገጽታ
ግንባታና ገቢ ማግኛ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ልዩ ፓኬጆቹ የሰሜንና የደቡብ የአገሪቷ የቱሪስት መስህቦችን ያቀፉ ናቸው፡፡ የሰሜኖቹ ላሊበላ ደርሶ መልስ፣ ባህርዳርና ጎንደር፣ አክሱምና ላሊበላ ሲሆኑ የደቡቦቹ አርባ ምንጭ ጂንካ ሙርሲ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ልዩ የፓኬጅ የጉብኝት ዋጋ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ በገዙት የቲኬት ዋጋ ላይ 100 ዶላር ብቻ የሚያስጨምር ነው፡፡ ለምሳሌ ለበዓል ጊዜ የተዘጋጀው ፓኬጅ ለ2 ቀን ላሊበላ ደርሶ መልስ ዋጋ 270  ዶላር ሲሆን በተጨማሪነት ለሚያዝ ዕቃ 39 ዶላር ያስጨምራል፡፡ ለፋይናንስ ጉባኤ ለመጡ እንግዶች የተዘጋጀው ልዩ ፓኬጅ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ በገዙት ቲኬት ዋጋ ላይ አንድ ሰው 100 ዶላር መጨመር ብቻ ነው ያለበት፡፡ ጎብኚው ከላሊበላ ወደ አክሱም መሄድ ቢፈልግ የሚጨምረው
25 ዶላር ብቻ ነው፡፡ በበዓላት ጊዜ ፓኬጅ ለ2 ቀን ቆይታ አንድ ጎብኚ ለባህርዳር ደርሶ መልስ የሚከፍለው 412 ዶላር ሲሆን በተጨማሪነት ለሚይዘው አንድ ዕቃ 39 ዶላር ይጨምራል፡፡ ለባህርዳር -ጎንደር የ3 ቀን
ቆይታ ደርሶ መልስ አንድ ሰው 581፣ ለሚይዘው አንድ ተጨማሪ ዕቃ 99 ዶላር ይከፍላል፡፡ በሰሞኑ
ልዩ ፓኬጅ ባህርዳር - ጎንደር ደርሶ መልስ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ በገዛው ቲኬት ላይ 100 ዶላር ብቻ መጨመር ነው፡፡ በበዓላት ጊዜ ፓኬጅ ከአዲስ አበባ አክሱም፣ ከአክሱም - ላሊበላና ከላሊበላ አዲስ አበባ የ3 ቀን ቆይታ 457 ዶላር፣ በተጨማሪነት ለሚያዝ አንድ ዕቃ 55 ዲላር ይከፈል ነበር፡፡ ለጉባኤ ለመጡት
እንግዶች የተዘጋጀው ልዩ ፓኬጅ በቲኬቱ ላይ 100 ዶላር መጨመር ነው፡፡ አንድ እንግዳ አራቱንም ፓኬጆች መጠቀም ቢፈልግ፣ በ100 ዶላሩ ላይ ለየመዳረሻዎቹ 25 ዶላር በመጨመር በ200 ዶላር
አራቱንም ፓኬጅ መጎብኘት ይችላል፡፡ ከአዲስ አበባ - አርባ ምንጭ በአውሮፕላን፣ ከአርባ ምንጭ ጂንካ ሙርሲ - አርባ ምንጭ በመኪና እንዲሁም ከአርባ ምንጭ  - አዲስ አበባ ለሚደረግ የአውሮፕላን በረራ ለ3 ቀን ቆይታ ጉብኝት የሚከፈለው 1100 ዶላር፣ በተጨማሪነት ለሚያዝ አንድ ዕቃ 56 ዶላር ነበር፡፡
ለጉባኤው የመጡ እንግዶች የሚከፍሉት 100 ዶላርና ለመዳረሻው ተጨማሪ 25 ዶላር እንደሆነ ታውቋል፡፡

Published in ዜና

    ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከግንቦቱ ምርጫ በኋላ አባሎቻቸውና ደጋፊዎቻቸው ላይ ግድያ፣ እስራትና እንግልት እየተፈፀመባቸው መሆኑን የገለፁ ሲሆን መድረክ 5 አባሎቹ እንደተገደሉበት ስታውቋል። ሰማያዊ ፓርቲም በአባላቱ ላይ እየተፈፀመ ነው ያለው ግድያ፣ እስርና እንግልት በአስቸኳይ እንዲቆም ሰሞኑን ጠይቋል፡፡ ድረክ በሰጠው በመግለጫ፤ በደቡብና በኦሮሚያ ክልሎች በአባላቱ ላይ የሚፈፀሙት እስራቶችና
ንግልቶች ተጠናክረው እንደቀጠሉ አመልክቷል፡፡ ከምርጫው በኋላ በትግራይ፣ በኦሮሚያ እና ቡብ ክልል ከተገደሉት 4 የመድረክ አባላት በተጨማሪ ሰኔ 27 ቀን በደቡብ ክልል በከፋ ዞን፣ ቢግንቦ ወረዳ፣ በኢዲዩ ካካ የምርጫ ክልል፣ በጎጀብ ምርጫ ጣቢያ የመድረክ ታዛቢ የነበሩት አቶ አስራት ኃይሌ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ግድያ እንደተፈፀመባቸው መድረኩ ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫ አመልክቷል፡፡
የሟቹ አስከሬን ከቀብር ቦታ ጋር በተያያዘም ከፍተኛ እንግልት አጋጥሞት እንደነበር የጠቀሰው መድረክ፤  እስከ ሐምሌ 1 ቆይቶ በህብረተሰቡ ትብብር የቀብር ስነ-ስርአቱ ሊፈፀም መቻሉን አስታውቋል፡፡ በተለያዩ የደቡብና የኦሮሚያ ዞኖችና ወረዳዎች በምርጫው የመድረክ ታዛቢ ወኪሎች የነበሩ፣ አባላት እና ደጋፊዎች ከፓርቲው ጎን በመቆማቸው ብቻ የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶች እንዳያገኙ ከመደረጉም በላይ ከፓርቲው አባልነት ራሳቸውን እንዲያገሉ ግፊት እየተደረገባቸው ነው ብሏል - መድረክ፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሰማያዊ ፓርቲ፤ “የወለደውን የረሳ ብሶት የወለደው ስርአት! የዘመቻ እስርና ግድያ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡” በሚል ሰሞኑን በፅ/ቤቱ በሰጠው መግለጫ፤ በግንቦቱ ምርጫ ማግስት በምርጫው በንቃት ይሳተፉ የነበሩ ዜጎች እየታደኑ እየታሰሩ ነው ብሏል፡፡ ፓርቲው፤ ዜጎችን በፖለቲካ አመለከታቸው ሳቢያ ከስራ ማፈናቀል፣ ማሰር፣ ማሸማቀቅና ማንገላታት እንዲቆም አበክሮ ጠይቋል።
“በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ የሰማያዊ፣ የመኢአድ፣ የቀድሞ አንድነት፣ የመድረኩና ሌሎችም የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ኢላማ ተደርገው እየተሳደዱና በጅምላ እየታሰሩ እንዲሁም በአሰቃቂ ሁኔታ እየተገደሉ ይገኛሉ” ብሏል - ፓርቲው በመግለጫው፡፡ ከምርጫው ማግስት ጀምሮ በተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ላይ እየደረሰ ነው ያለው ግድያ፣ እስርና እንግልትም በአስቸኳይ እንዲቆም ሰማያዊ ፓርቲ ጠይቋል፡፡  

Published in ዜና

ከአፍሪካ 7ኛ ደረጃ ተሰጥቷታል (አፍሪካን ክራድል)

  ኢትዮጵያ በዓለም የሀብት ደረጃ ከ184 ሃገራት 171ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሲሆን የመንግስት ሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት “አፍሪካን ክራድል” የተሰኘ ድረገፅን ጠቅሶ ከአፍሪካ 10 ሀብታም ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ በ7ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች ብሏል። የዓለም የሃብት ደረጃ አለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት ከ2009-2013 ሃገራት በየዓመቱ ያስመዘገቡትን አጠቃላይ የሃገር ውስጥ ምርት እድገት (GDP) መሰረት አድርጎ ያወጣው እንደሆነ ታውቋል፡፡ የዓለም ቁጥር 1 ሃብታም ሃገር የተባለችው ኳታር ስትሆን ሉክዘምበርግና ሲንጋፖር በ2ኛ እና 3ኛነት ደረጃ ይከተላሉ፡፡ ታላቋ ሃገር አሜሪካ ደግሞ በ7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡ በዓለም ሃብታም ሃገራት ዝርዝር ሲሸልስ 38ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሲሆን ከአፍሪካ ሃገራት የ1ኛነት ደረጃ ይዛለች፡፡ ሲሸልሰን ተከትላ ኢኳቶሪያል ጊኒ ከዓለም በ40ኛ ደረጃ፣ ከአፍሪካ በ2ኛ
ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ ከአፍሪካ ሃገራት በቀዳሚነት ከተሰለፉት መካከል ቦትስዋና፣ ጋቦን፣ ሞሪሽየስ፣ ሊቢያ፣ ደቡብ አፍሪካና ቱኒዚያ ይገኙበታል፡፡ በዓለም የሃብት ደረጃ፣ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሃገራት በ45ኛ ደረጃ ላይ ስትገኝ በእነ ደቡብ ሱዳን፣ ቻድ፣ ጅቡቲ፣ ሱዳን፣ ኡጋንዳ፣ ኬንያ፣ ሞዛምቢክ፣ ሩዋንዳ እና ሴራሊዮንን በመሳሰሉ ሃገራት ተበልጣለች፡፡ በሌላ በኩል “አፍሪካ ክራድል” የተሰኘው ድረ ገፅ ያወጣው የአፍሪካ አገራት የሃብት ደረጃ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ካወጣው ዝርዝር ጋር እንደማይጣጣም ለማወቅ ተችሏል፡፡በ“አፍሪካ ክራድል” መረጃ መሰረት፤ ከአፍሪካ ሃገራት በሃብት 1ኛ ደረጃ የተሰጣት ደቡብ አፍሪካ ከ10 በላይ በሆኑ የአፍሪካ ሃገራት ተቀድማ በዓለም 80ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ ጎረቤት አገር ኤርትራ ከዓለም 180ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሲሆን ላይቤሪያ 181ኛ፣ ቡሩንዲ 182ኛ፣ ዚምባቡዌ 183ኛ፣ ኮንጎ ኪንሻሣ 184ኛ ደረጃን በመያዝ በሃብት የመጨረሻዎቹ አገራት ሆነዋል፡፡ የ“አፍሪካን ክራድል” ጥናት የሃገራት አመታዊ ምርትን (GDP) መነሻ ያደረገ ሲሆን ደቡብ አፍሪካ በዓመት 595.7 ቢሊዮን ዶላር በማስመዝገብ 1ኛ ስትሆን፣ ግብፅ 551.4 ቢሊዮን ዶላር፣ ናይጄሪያ 478.8 ቢሊዮን ዶላር፣ አልጄሪያ 284.7 ቢሊዮን ዶላር፣ ሞሮኮ 180 ቢሊዮን ዶላር፣ ቱኒዚያ 108.4 ቢሊዮን ዶላር፣ ኢትዮጵያ 108.2 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም ሱዳን 89.97 ቢሊዮን ዶላር አመታዊ ገቢ በማግኘት የአፍሪካ 10 ሀብታም ሃገራት ተብለዋል ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ድረ - ገፁን ጠቅሶ ያስቀመጠው መረጃ ያመለክታል፡፡

Published in ዜና

ኢትዮጵያ የግመል ወተት ወደ ውጭ በመላክ እየተገባደደ ባለው የበጀት ዓመት ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ እንደምታገኝ የስጋና ወተት ልማት ኢንስቲትዩት መረጃ ጠቆመ፡፡ የግመል ወተት ወደ ውጪ ቢላክ ከፍተኛ ጥቅም እንደሚያስገኝ ተገንዝባ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ 3 የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት በመላክ ገቢ ማግኘቷም ታውቋል፡፡ ሃገሪቱ ዘንድሮ ለፑንትላንድ፣ ሶማሌ ላንድና ጅቡቲ የግመል ወተት የላከች ሲሆን እነዚህ አገሮችም የኢትዮጵያን የግመል ወተት ወደውት ለመሸመት ፍላጎት አሳይተዋል ተብሏል፡፡
በአሁን ሰዓት አንድ ግመል እስከ 6 ሊትር ወተት በቀን የምትሰጥ ሲሆን የአንድ ሊትር ዋጋ ከ400 ብር በላይ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ሃገሪቱ ወደፊት የግመል ሃብቷን በአግባቡ ከተጠቀመች፤ ከግመል ወተት ከፍተኛ ገቢ ልታገኝ እንደምትችል ኢንስቲትዩቱ ተንብየዋል፡፡

Published in ዜና
Page 8 of 17