አምስት በአማርኛና አንድ በኦሮምኛ ቋንቋ የተፃፉ ስዕላዊ ባለቀለም የህጻናት መፃህፍት ተዘጋጅተው የታተሙ ሲሆን በነገው ዕለት ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ ከደንበል ህንፃ ፊት ለፊት፣ ከዴሉክስ ፈርኒቸር ጀርባ በሚገኘው ኢግሉ አይስክሬም ቤት ይመረቃሉ፡፡
የመፃህፍቱን ታሪኮች በመድረስ አዜብ ወርቁ፣ ዳንኤል ወርቁ፣ ሰላማዊት ሙሉጌታና ሲሳይ ተስፋዬ የተሳተፉ ሲሆን የስዕል ስራዎቹን የሰሩት ሰዓሊ ደረጄ ደምሴ፣ አርክቴክት አሃዱ አባይነህና የህፃናት ስዕል ባለሙያው ይስሃቅ ሳህሌ እንደሆኑ የመፃህፍቱ አሳታሚ “ሚዳቆ ፐብሊሺንግ” ለአዲስ አድማስ በላከው ጋዜጣው መግለጫ ጠቁሟል፡፡ የመፃህፍቱ ዋጋ (እያንዳንዱ) 29 ብር ነው ተብሏል፡፡ “ሚዳቆ  ፐብሊሺንግ” ዋነኛ ትኩረቱን በህፃናት መፃህፍት ላይ ያደረገ የህትመት ተቋም እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ከሽብርተኝነት ጋር በተያያዘ የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸው በማረሚያ ቤት የሚገኙት የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የቀድሞ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አንዷለም አራጌ በማረሚያ ቤት ሆነው ለሁለተኛ ጊዜ የፃፉት “የሀገር ፍቅር ዕዳ” መጽሐፍ ለንባብ በቃ፡፡
አቶ አንዷለም አራጌ ከዚህ ቀደም “ያልተሄደበት መንገድ” የተሰኘ መጽሐፍን ለአንባቢያን ያደረሱ ሲሆን “የሀገር ፍቅር እዳ ከቀሳ ጐንደር እስከ ቃሊቲ አስር ቤት” የተሰኘው አዲሱ መጽሐፋቸው በ32 ምዕራፎች ተከፋፍሎ፣ በ400 ገፆች የቀረበ ነው፡፡ ዋጋው 100 ብር ነው፡፡

 “… ከገራገር ህይወቷ ላይ የሚከተላት ምሳሌ የፍስሃዋን በር የሚዘጋ ነገር አታጣም፡፡ በተፈጥሮ ያልሆነ በልጅ ሃሳብም ያልሆነ፣ በሴትነትም ያልሆነ የሚከተላት ጠልና ጥል እጇ ላይ ነጥሮ ይመጣል፤ አነጣጥሮ ይመታታል፡፡ በሩን ወደ ኋላ ዘጋችው። አይኖቿን ጨፍና አመታቱን አሰበች፡፡ ጠባሳዋን ቆጠረች፡፡ …”
(ከመፅሀፉ የተቀነጨበ)
በደራሲ ሊና ካሳሁን የተፃፉ ታሪኮችን ያካተተው “ፍቅር እና አደራ እና ሌሎችም” የተሰኘው መፅሃፍ ሰሞኑን ለአንባቢያን የቀረበ ሲሆን በዛሬው እለት ከቀኑ 9 ሰዓት ጀምሮ ከሬዲዮ ፋና ህንፃ ጀርባ በሚገኘው ወመዘክር አዳራሽ ይመረቃል፡፡
መፅሀፉ 11 ታሪኮችን የያዘ ሲሆን በ162 ገፆች እንደተቀነበበና በ40.50 ለገበያ መቅረቡ ታውቋል። የደራሲዋ ተከታይ ስራም “የእሳት እራት” የሚል ርዕስ ያለው እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡

በይግረም አሸናፊ የተፃፉ የልብወለድ እና ወጎች ስብስብ የያዘው “ክብሪት” ለገበያ ቀርቦ እየተነበበ ነው፡፡ በ137 ገፆች  20 ታሪኮችን ያካተተው መፅሃፉ፤ በብር 45.62 ለገበያ ቀርቧል፡፡

  በደራሲና ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ለገሰ ተፅፎ የተዘጋጀው “ያየ ይፍረደው” የተሰኘ የቤተሰብ ፊልም ባለፈው ማክሰኞ በአቤል ሲኒማ አዳራሽ ተመረቀ። በአልዩ ፊልም ፕሮዳክሽን የቀረበው ፊልሙ፤ የ1፡30 ርዝመት ያለው ሲሆን ፊልሙን ሰርቶ ለማጠናቀቅ 7 ወር እንደፈጀ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በፊልሙ ላይ ተዋንያን ቴዎድሮስ ለገሰ፣ አዚዛ አህመድ፣ ህፃን ማርያማዊት ፍፁም፣ ሔኖክ ብርሃኑና ሌሎችም አንጋፋና ወጣት ተዋንያን ተሳትፈውበታል፡፡

 ሀገሬ ሚዲያ ኮሙኒኬሽን፤ የደቡብ ጎንደር የቱሪዝም ማውጫ ዳይሮክተሪ አዘጋጅቶ አሳተመ፡፡ ማውጫው በ10 ወረዳዎችና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች ግዛት ውስጥ የሚገኙ ከ100 በላይ ተፈጥሮአዊ፣ ባህላዊ፣ ታሪካዊና መንፈሳዊ መስህቦችን ያካተተ ነው ተብሏል። ከመስህቦቹ ውስጥ 80 በመቶው ከ250 ዓመት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረ ሲሆን ከ50 በመቶ የሚበልጡት ደግሞ ከ500 ዓመት በላይ ዕድሜ ያላቸው ታሪካዊ ቅርሶች እንደሆኑ ታውቋል፡፡
ማውጫው ሥፍራዎቹን ለመጎብኘት የሚያስችሉ መረጃዎች እንዲሁም የትራንስፖርትና ሌሎች አገልግሎቶች የሚገኙባቸውን አግባብ በሚጠቁም መልኩ መዘጋጀቱን የጠቆሙት አሳታሚዎቹ፤ ዳይሬክተሪው ከቱሪዝም ልማት ጋር ትስስር ላላቸው አካላት፣ ለቤተ - መፃህፍትና መንግስታዊና መንግስታዊ ላልሆኑ ተቋማት በነፃ እንደሚታደል ገልፀዋል፡፡
ሀገሬ ሚዲያ ኮሙኒኬሽን፤ በቱሪዝምና ባህል ላይ አተኩሮ የሚሰራ ተቋም ሲሆን ከዚህ ቀደም የሰሜን ሸዋ ዞን ቱሪዝም ዳይሮክተሪ፣ የኢትዮጵያ ተፈጥሮና ፓርኮች ማውጫ፣ የኢትዮጵያ ሙዚያም ማውጫና የኢትዮጵያ ፌስቲቫል ማውጫ አዘጋጅቶ ማሳተሙ ይታወቃል፡፡

ለአዘጋጁ የተሰጡትን መረጃዎች ለመሰብሰብ 7 ዓመት ፈጅቷል
                                          ዓለማየሁ ገላጋይ
     አንዳንድ ጊዜ ለወግ የማያመች ሁኔታ ይፈጠራል። ትዝ ይለኛል የዛሬ አስር ዓመት ገደማ ስለ ደበበ ሰይፉ ለመፃፍ ሳስብ ተማሪው ጀማነሽ ሰለሞንን በአጋጣሚ አገኘኋት፡፡ የደወለችልኝ ሌላ ጓደኛዬ ነበረች፡፡ ሶስና ዳንኤል ትባላለች፡፡ በወቅቱ የተለያዩ ቴአትሮች ላይ ትተውን ነበር፡፡ እሷን ለማግኘት ስሄድ ጀማነሽ አብራት ተቀምጣ አገኘኋት፡፡ ለዚህ አመክንዮአዊ ዓለም የማይዋጥ ገጠመኝ ነበር፡፡ አደግድጎ ሀሳብና ምኞታችንን የሚያደላድል አጋፋሪ አምላክ ይኖር ይሆን? አንዳንዴ በልባችን ያሰብነው ሰው ስልክ ይደውልልናል፣ ሌላ ጊዜ ያነሳነው ሰው አውግተን ሳንጨርስ ይመጣል …
ሶስና አስተዋወቀችን፡-
“እሱ አለማየሁ ይባላል፡፡ የኔሽን ጋዜጣ ጋዜጠኛ ነው፡፡ እሷ ደግሞ …
“እኔ እንኳን አውቃታለሁ” አልኩ፡፡
እኔን ማወቅህ አይደንቅም በማለት አይነት ዝም አለችኝ፡፡  በእርግጥም ስለመታወቋ የት? እንዴት? … ማለት አይጠበቅባትም፡፡ ጀማነሽ ናታ!
“ከልቤ ሳስብሽ ነው ያገኘሁሽ” አልኳት፡፡ ተዓምር የተመረኮዘ ባህታዊ ወይም ልዩ ትኩረት ፈላጊ ጉርባ እመስላት ይሆን?
በግርምት አየችኝ፡፡ አይኖቿ የአንደበቷን ያህል ውብ ድምፅ አላቸው፡፡ ከወፍ በመቀጠል ዘምረው ለመኖር ብቻ የተፈጠሩ ጥንዶች፤ ያለ ግብራቸው እንክብል ድምፆች እያነቡ ህይወትን ጨሌያማ አሸብራቂ የሚያደርጉ አይኖች----
 ስለ ምን በልቤ እንዳሰብኳት ነገርኳት፡፡
“ው … ይ፤ ስለ ጋሽ ደቤ ልትፅፍ ነው?” አለች፡፡ ያ በየሬዲዮውና በየመድረኩ የማውቀው ድምፅ መጣ፡፡ ይሄ ድምፅ ለብዙ ተዋናይ ሴቶች ተፅዕኖው አይሎባቸው ተናጥላዊውን የተፈጥሮ ችሮታ ንቀው፣በመምሰል መፍጨርጨር ውስጥ እንዲያልፉ አስገድዷቸዋል፡፡ ለምሳሌ መስታወት አራጋው….!!
ጀማነሽ፤ “ጋሽ ደቤ፣ ጋሽ ደቤ፣ ጋሽ ደቤ…” የበዛበት ጨዋታዋ ልቤን ወደ ሌላ መራው” ከመጣጥፍ ይልቅ መፅሐፍ ወደማዘጋጀት፡፡ ገጣሚው ደበበ፣ መምህሩ ደበበ፣ ተመራማሪው ደበበ፣ ፀሐፌ ተውኔቱ ደበበ … ከዚያ በላይ ደግሞ ሰው የሆነው ደበበ፡፡ ሐሜት የሚወጋው፣ ሽሙጥ የሚሸረክተው፣ አቃቂር የሚፈልጠው… ደበበ፡፡ አንዳንዴ የዩኒቨርሲቲ ግቢውንና ግቢኛዎቹን ምን እንዲህ አወረዳቸው? የሚያሰኝ ተራ ሐሜት፣ መናኛ ሽሙጥና የነተበ አቃቂር ይደመጣል፡፡ በተለይ ከወደ መንግሥቱ ለማ አቅጣጫ …
… እናም (ጀማነሽ ስትነግረኝ) ደበበ (ጋሽ ደቤ) በተለይ  ተማሪዎቹ የተራው ሐሜት ማስተጋቢያ መሆናቸው ይቆጨዋል፡፡ አንድ ቀን ከወትሮው በተለየ ስሜቱ ተጎድቶ ወደ ክፍል ገባ፡፡ ደበበ ሲያስተምር ከመደበኞቹ ተማሪዎች በተጨማሪ “ቃራሚዎቹም” ክፍሉን ይሞሉታል፡፡ ለተወሰነ ደቂቃ ዝም ብሎ ክፍሉን ሲመለከት ቆየ፡፡ ዘወር ብሎም ሁለት ቃላቶች ጥቁር ሰሌዳ ላይ ፃፈ፡፡ “ቀጭን” እና “ወፍራም” ይላል የፃፈው። በመቀጠል እንዲህ ሲል ጠየቀ፡፡ “እስቲ አንዲት ቀጭን ሴት የምትመሰገንበትና የምትወደስበትን ቃላት ንገሩኝ” አለ፡፡
ተማሪዎች ታዘዙ፡-
“ሐመልማል” አሉ
“ጥሩ!” አለ
“ቀጭን እመቤት”
“ሌላ?” ብሎ ቢጠብቅም አልተገኘም፡፡ “እሺ የምትሰደብበትን ንገሩኝ”
“በልታ የማትጠረቃ!”
“እሺ”
“ሲባጎ!”
“እሺ”
“አፍንጫዋን ቢይዟት የምትሞት!”
“ሌላ?”
“አንድ ሀሙስ የቀራት፣ ቀትረ ቀላል …”
ከሀምሳ በላይ ስድብ ተሰብስቦ በ “በቃ” ቆመ፡፡
“አሁን ደግሞ ወፍራሟን አሞግሱ”
“ድንቡሼ፣ ሞንዳላ፣ ሰውነተ ሙሉ…” ጥቂት ተብሎ መቀጠል ሳይችል ቀረ፡፡
“አሁን ደግሞ ስድቧን እንይ; አላቸው፡፡
“በርሜል፣ ድብኝት፣ ዘረጦ፣ ድብክብክ፣ ዝፍዝፍ፣ ሞፎ፣ ገንፎ …”
“በቃ! በቃ! አያችሁ፣ ባህላችን ለማወደስና ለማድነቅ ሽምድምድ ነው፡፡ ከዚያ ይልቅ ለስድብ፣ ለሽሙጥ፣ ለማንኳሰስና፣ ስሜት ለመጉዳት የበለፀገ ነው፡፡ እናንተ የዚህ ተሳታፊ ከመሆን ይልቅ ለመለወጥ መጣጣር ነበረባችሁ፡፡”
የዚያን ቀን ሳያስተምር ጥሎ ወጣ፡፡ ከዚህ በላይ ትምህርት አለ? ጀማነሽ ጥሩ አስተዋይ ብቻ ሳትሆን ግሩም ተርጓሚ ናት፡፡ ገጠመኞቹን በጥሬው ሳይሆን ከእነ ትርጓሜው ታወሳለች፡፡ የደበበ ሰይፉ ውጣ ውረድ እንደ ፎቶ ግራፍ ግለሰብ ወካይ ብቻ አይደለም፡፡ የህብረተሰብ ጥሪት ብሎም የሀገር ሀብት ሊሆን የሚችል ነው - የወል፡፡ ታዲያ እንዴት የዚህ ጉምቱ ገጣሚ ህይወትና ክህሎት ሳይጠናቀር ቀረ? በምን ቢያንስ? ወይም በምን ብናንስ?
ደበበ ሠይፉ ከህይወት ባሻገር በክህሎትም የሥነ ጽሑፉ ቁንጮ ነው፡፡ “የብርሃን ፍቅር” እና “ለራስ የተፃፈ ደብዳቤ” ከተሰኙ የግጥም መጽሐፍቱ ባሻገር በፀሐፌ ተውኔትነቱም ስድስት ያህል ሥራዎችን አበርክቷል። ባለ አንድ ገቢር ተውኔቶቹ፡- “ሳይቋጠር ሲተረተር”፣ “እነሱ እነሷ”፣ “ከባህር የወጣ ዓሣ”፣ “እናትና ልጆቹ”፣ “እድምተኞች” እና “ክፍተት” ይሰኛሉ፡፡ ከእነዚህ ስራዎቹ በተጨማሪ በግጥምም ሆነ በተውኔት ላይ ልዩ ልዩ ጥናቶችን አቅርቧል፡፡ ታዲያ ምኑ ከማን አንሶ፣ ህይወትና ክህሎቱ ሳይደርሰን ቀረ? በምን? ለምን?
ሰባት ዓመታት ያህል ወደ ኋላ ልመልሳችሁ ነው። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋዎች ጥናት ተቋም፣ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ክፍለ ትምህርት አንድ የጥሪ ደብዳቤ በትኖ ነበር፡፡ የደብዳቤው ዓላማ በደበበ ሰይፉ ሥራዎችና የሕይወት ታሪክ ላይ ውይይት በማድረግ እየተዘጋጀ ላለው መጽሐፍ ግብአት መሰብሰብ ነበር፡፡
ዓላማውም ግቡም የሚያስቀር አልነበረምና በዕለቱ (ሚያዝያ 14 ቀን 2000 ዓ.ም) ባህል ማዕከል ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ተገኘሁ፡፡ በደበበ ሰይፉ ሥራዎችና የህይወት ታሪክ ላይ የሚያተኩረውን መጽሐፍ የሚያዘጋጁት አቶ ገዛኸኝ ጌታቸው ወደ መድረኩ ወጡ፡፡ መጽሐፉን የማዘጋጀት ተግባሩ በመካሄድ ላይ እንዳለ በመግለጽ፣ የደረሱበትን ሁኔታ አስታወቁን፡፡ በደበበ ቤተሰቦች ድጋፍ ታፍሮና ተከብሮ የቆየው የደበበ የቤት ውስጥ ቢሮ ተከፍቶላቸው ግብአቶችን ማሰባሰባቸውን አወሱን። ሌላው ቀርቶ ደበበ አውልቆ የሰቀለውን ኮት ከስምንት አመት በኋላ እንዲፈትሹ የተፈቀደላቸው እሳቸው ብቻ መሆናቸውን ገለፁ፡፡ ቢሮው ውስጥ የተገኙት ወረቀቶች እጅግ ጠቀሜታ ያላቸውና ብቸኞችም እንደሆኑ በድፍኑ አስረዱን፡፡ አንዳንድ የተገኙ ወረቀቶች የደበበን ጉዳትና በደል የሚመለከቱ የግል ማስታወሻዎች ናቸው ተባልን። እነዚህ ማስታወሻዎችና ያልተላኩ ደብዳቤዎች ውስጥ የተጠቀሱ ታዋቂ ሰዎች ስማቸው ለተወሰኑ ዓመታት ተገድፎ ትውልድ ካለፈ በኋላ እንዲካተቱ መወሰኑን አወሱን፡፡
በዚህ ክብደት የተጀመረ ሌላ የህይወትና የጥበብ ሒስ መጽሐፍ እንዳለ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ “የአረንጓዴው ዘመቻ” አይነት ዝግጅት፣“የቀይ ኮከብ ዘመቻ” አምሳያ መቆርቆርና ቁጭት ተንፀባረቀ፡፡ ታዳሚዎች ስለ ደበበ ያላቸውን ገጠመኝ ወረወሩ። በአደባባይ ለማይናገሩ ስልክ ቁጥር የሚሰፍርበት ቅጽ ተበተነ፡፡ ምን ይፈጠር ይሆን? አልን፡፡ የማይጠቀሱት የደበበ ደመኞች እነማን ይሆኑ? አልን፡፡ መጽሐፉ መቼ ይጠናቀቅ ይሆን? አልን--
ከአመታት ጥበቃ በኋላ የቀይ ኮከብ ዘመቻ አምሳያው የመጽሐፍ ዝግጅት በቀይ ኮከብ አምሳያነት ከሸፈ ተባልን፡፡ ፀሐፊውም በጓድ መንግሥቱ አምሳያነት ከአገር “ፈረጠጡ” ተባልን። እንዴት? ለምን?...ማንም ያወቀ ሰው አልነበረም፡፡
“የማያዛልቅ ማህበር በጠጅ ይጀመራል” ነው ነገሩ፡፡ ቀድሞውንስ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እዚህ ጉዳይ ውስጥ ገብቶ ማፈድፈድ ነበረበት? አንድ ሰው የአንድን ግለሰብ ታሪክ ሲጽፍ በራሱ አግባብ የራሱን መረጃ ያሰባስብ እንጂ ዩኒቨርሲቲው እንደ “አረንጓዴው ዘመቻ” ሰብስቦ መፈክር እንዲሰማ ማደላደል ነበረበት? ደግሞስ ተቋሙ እዚህ ውስጥ እጁን ካስገባ ፍፃሜውን የመከታተል ግዴታ የለበትም? ግለሰቡ ከየአቅጣጫው ያሰባሰቡትን መረጃ እና መዛግብት ይዘው ከሀገር ሲወጡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አይጠየቅም ነበር? ብዙ የቁጭት ጥያቄዎች አሉ፡፡
በደበበ ህይወትና ሥራዎች ላይ የሚያተኩረው መጽሐፍ ከፉከራ ግብአትነት ሳያልፍ ሰባት አመት ከሦስት ወር አለፈው፡፡
ባለፈው ሐምሌ 5 የደበበን 65ኛ ዓመት የልደት ቀን በማስመልከት ወንድሙ ዘንድ ስልክ መትቼ ነበር፡፡ ለሰባት ዓመታት ድምፁ ጠፍቶ የቆየው የደበበ መጽሐፍ ጉዳይ አሁን ተስፋ እንዳለው ተነገረኝ፡፡
“እንዴት?” አልኩ፡፡
“የተሰባሰበውን ዶክመንት ለማግኘት በኢሜይልና በስልክ አፈላልገን ምላሽ አጥተን ቆይተን ነበር፡፡ በኋላ ቢቸግረን ካናዳ የሚኖር ዘመድ ልከን፣ መጽሐፉን የሚያዘጋጀውን ሰው በግንባር እንዲያናግረው አደረግን። በመጨረሻ ዶክመንቱ ተመልሶልን እኛ እጅ ይገኛል፡፡”
ይገርማል፤ የደበበ ቤተሰቦች ከሰባት ዓመታት በኋላ መጽሐፉን የሚያጠናቅር ሌላ ሰው በማፈላለግ ላይ ናቸው፡፡ ይሄ በደል አይደለም? በደልነቱ ከቤተሰብነት አልፎ የአገር አቀፍነት ንክኪ የለውም? ጉዳዩ የሚያሳስብስ አይሆንም? “እንጀራ” ይሉት ጢያራ እየነጠቀ በወሰደብን ምሁራን ስንት ውጥናችን ጨንግፎ ይሆን? መጽሐፍ ጽፎ ሃሳብ ከማድረስ፣ በባዕድ አገር ታክሲ እየነዱ ህዝብ ማመላለስ እንዴት በለጠ? በምን? እዚህ ውስጥ የክብር ጥያቄ የለም? የቃልስ? ይደክማል! የዘመኑ ነገር ይደክማል!!

Published in ጥበብ
Saturday, 18 July 2015 11:51

ፈረሰኛው ፍቅር!

እሳሩ ቤት፣ምድጃ ዳር ተቀምጦ፣ ያለ ወትሮው ቢላ በሞረድ ሲስል ያዩት አያቱ ደስ አላላቸውም። “የመድኃኒዓለም ያለ! አንተ የምን ቢላ ነው የምትስለው!” ሲሉት ድንገት ቀና ብሎ አያቸውና መልሶ አቀረቀረ፡፡ እማማ ዝናብዋ ከቤተክርስቲያን መመለሳቸው ነው፡፡
“ስማ እንጂ ጉልላት…አትናገርም እንዴ?” አሉ ነገሩ ስላልገባቸው፡፡ ዐውደ አመት አይደለ፤ የታቦት ንግስ የለ!...እና ቢላ መሳልን ምን አመጣው በሰንበት!...
“አይ፤ ዝም ብዬ ነው፡፡” አለና ብድግ ብሎ ወደ ውጭ ወጣ፡፡ የሳር ቤትዋ በር እያስጎነበሰችው ነው፡፡ የዛሬ ሶስት ዓመት ከጂማ ሲመጣ እንዲህ አልነበረም። ሳያጎነብስ እንደ ልቡ ወጥቶ ይገባ ነበር።
አያቱ ከቤተክርስቲያን ሲመለሱ እሳቸውን ተከትለው አባ ሲርመታ፣ ጋሽ አሰፋና ሌሎችም አዛውንቶች ይመጣሉ፡፡ ይህ በየሳምንቱ የተለመደ፣ የየሳምንቱ የሕይወት ቀለበት ነው፡፡ ቀኑ እንደሆነ ዞሮ ይመጣል - ይሄዳል፡፡ ክቡ አያልቅም። የሰውን የሩጫ ዙር እያስጨረሰ፣ እያደከመ አሸንፎ ይቀጥላል፤ ሰው ነው አለክልኮ የሚያበቃው፡፡ ይኸው ጉልላት ከመጣ እንኳ በየሳምንቱ እሁድ በተስኪያን ይሄዳሉ፣ ይመለሳሉ፤ ከዚያ ቡና ይጠጣሉ፤ በየወሩ ደግሞ የመድሃኔዓለምን ጥዋ ይጠጣሉ፡፡ …ቀኑ ያው ነው….
“ሁኔታህ አላማረኝም!” አያቱ፡፡  ድምፃቸው ተከተለው፡፡ ውጭው ለስላሳ አረንጓዴ ምንጣፍ መስሏል፡፡ ሲያዩት ብቻ ሳይሆን ሲረግጡት ይመቻል፡፡ በስተቀኝ ትንሽ ራቅ ብሎ፣ ከጐጆዋቸው ጀርባ ያለችው ግራር ዛፍ መሬት ላይ ክንፎችዋን እንደ ጃንጥላ  ተክላለች፡፡
ጓሮው በደረሰ እሸት በቆሎ ግጥም ብሏል፡፡ ራቅ ሲል ከዚህች ተራራ ሥር ዙሪያውን ያሉት ሜዳማ ስፍራዎች ሁሉ፣ አረንጓዴ ቀለምና የዝርግ ውሃ ውበት ጠግበዋል፡፡ ሁሉም ነገር ያምራል፡፡ ማዶውን የነጭ ፈረስ ጭራ መስለው በሩቅ የሚታዩት ሁለት ፏፏቴዎች ልብን ይጣቀሳሉ፡፡
ሰፈራቸው የሚኖሩት ሰዎች በአብዛኛው ክርስቲያኖች ስለሆኑ ሠፈሩ ጭር ብሏል፡፡ ከነርሱ ጐጆ የሜዳውን ክብ ተሻግሮ ያሉት ወይዘሮ ተዋበች - ድንገት ከወደ መድሃኔአለም ብቅ ሲሉ ሰላም ላለማለት ቀኙን በነፉንጐ ቤት ጐን ታጠፈ፡፡
እሁድ ባይሆን ኖሮ ይሄኔ ወፍጮ ላይ አጐንብሳ እህል እያጐረሰችው፣ መጁን ስትነዳ የምታንጐራጉረው ዜማ ልቡን ያማስለው ነበር። ዛሬ ግን የለችም፤ አባትዋ መምሬ ካሳ ሰንበትን ቤተክርስቲያን እንድታሳልፍ ነግረዋታል፡፡
የእርሱ እያት ዝናብዋም እሁድ በተስኪያን ቢስምላቸው ደስ ይላቸዋል፡፡ የልጃቸው ልጅ ሳይጦር ሳይቀበራቸው ሃይማኖቱን እንዲቀይር አይፈልጉም፡፡ ለዚህም ሁሌ ቸሩ መድኃኒዓለምን እንደጐተጐቱ ነው፡፡ ቸሩ መድኃኒዓለም የላንፉሮ ታቦት ነው፡፡ ላንፉሮ ደግሞ የደጃች ባልቻ ርስትና መንደር ናት፡፡
የመድኃኒዓለም ደብር ዙሪያውን በከበባት ዝርግ መልክዐ-ምድር መሀል ላይ እንደ መሶበወርቅ ጉብ ባለው የላንፉሮ ሻኛ ላይ ተሰይሞ፣ ግራና ቀኙን ቁልቁል የሚያይ ነው የሚመስለው፡፡
ጉልላት ወዲያ ወዲህ ተንጐራደደና የሳለውን ቢላ ወስዶ አድባሩ ዛፍ ሥር ሸጐጠው፡፡
“ዛሬ ያለወትሮው ሊጨክን ነው፡፡
“ጉ-ሌ አንተ” ተጣሩ ዝናብዋ፡፡
“እሜት!” ሲል ተቆጡ፡፡ “እዚያ ደግሞ ምን ታደርጋለህ?...ና ውጣ! በሽታ ለይ እንዳትወድቅ እዚያ አትሂድ አላልኩህም?”
“ቤዛንኩሉ ዓለም - ቤዛንኩሉ ዓለም - ተወልደ…እህህህ…ኦሆ - ኦሆ ኦሆ”
ልቡ ደረቱን ሰንጥቃ፣ አየር ላይ የበረረች መሰለው፡፡ የሚጣፍጥ - ድምፅ የሚነካ ዜማ ፉንጐ ናት፡፡ ፉንጎ ከቤተክርስቲያን እንደመጣች የሰማችውን ዜማ አወረደችው፡፡
 መንፈሳዊ ቅኔ ምን እንደሆነም አያውቅ!...ከማረቆ ነው የመጣው፡፡ ከጂማ ከመጣ በኋላ ለአንድ ዓመት ማረቆ የመኪና ጭራ ሲከተል ቆይቶ ነበር፡፡ እዚያ የኖረው ከታላቅ እህቱ ጋር ነበር፤ ለሃይማኖት እምብዛም ነው፡፡ እንዲያውም ወደ ዘፈን ያደላል፡፡ ማምሻ-ማምሻ ጨረቃ የወጣች ሰሞን ከቤታቸው ፊት ለፊት ካለችው ዛፍ ሥር ቆሞ በፉጨት ሲዘፍን፣ ፉንጐ እቤት ውስጥ ሆና ስቅስቅ ብላ ታለቅሳለች፡፡ ዘፈኑ ይሁን ፍቅሩ ግን አልገባትም፡፡ እሱ በድምጽዋ፣ እሷ ደሞ በፉጨቱ ተጠላልፈዋል፡፡
እሷማ ጭፈራም ስትችልበት ለብቻ ነው፡፡ ላሌ-ሄቦላሌ ቦላሌ ስትል ከሠማይ ከዋክብት የሚረግፉ ይመስላል፡፡ ጨረቃም መቀነትዋን ፈትታ አብራት የምትጨፍር ይመስላል፡፡
እማማ ዝናብዋ ደሞ ሞያዋን ያደንቁላታል። “አቤት የምትሠራው ወጥ!…የዘመዶችዋን ይዛ…አባትዋ ከመንዝ ነው የመጡት፣ እናትዋ ያገራችን ሰው ናት…ትንሽ የማልወድላት እንደ ወንድ ፈረስ መጋለብዋ ነው፡፡” ይላሉ፡፡
ይሄኔ ፍቃዱ ይብስበታል፡፡ አንዳንዴ እርሱ ከብቶች ሊያሰማራ ወደ ዓባያ ሀይቅ ሲሄድ እርሷ ከቡሬ ውሃ ቀድታ ስትመጣ ይገናኛሉ፡፡ ንቁ ናት፡፡ ሰማያዊ ጀርሲ ቀሚስዋን በአዘቦት ቀን አትለብስም። የመድሃኔዓለም ንግስ ወይም የጥምቀት ቀን ነው የምትለብሰው፣ የክት ናት፡፡ አዘውትራ ቀይ ሻማ ውስጥ ልብስዋን ነው የምትለብሰው፡፡ ታዲያ ሁሌም ሲያገኛት ዘፈንዋን እንዳቀለጠችው ነው፡፡ መዝፈን፣ መጨፈር ትወዳለች፡፡ ሠርግ ቤት፣ ጥምቀት በዓል ላይ፣ ሰው ሁሉ ቆሞ ያያታል፡፡
“ፉንጐዬ”  ይላታል፡፡
“አቤት ጉሌ!”
አይንዋን ያያታል፣ ጐንበስ ትላለች፡፡
“ሰው እንዳይመጣ!”
“ይምጣአ!”
“እማማ ዝናብዋ ቢመጡስ?”
“ምንም አይሉኝም፡፡”
“ውሸታም!”
“እኔ ልሙት!” የእጅዋን መዳፍ በእጁ መዳፍ ይመታና፣ በሰበቡ መሀል መዳፍዋን ይስማታል፡፡
“ኧረ ተው” ትለዋለች፡፡ ፈገግታዋ ግን ከልብ እንዳልሆነ ያስታውቃል፡፡ …የእጅዋ መዳፍ ግን በስራ የደደረ ነው፡፡ ቢሆንም የልብዋ ልስላሴ ያንን ያስረሳዋል፡፡
ፉንጎ ፀጉርዋን በስልጤ ብሔረሰብ ባህል መሠረት ሲጃ ተሠርታ፣ ከፊት - ለፊት እንደ እርከን የቆመ ፀጉርዋ ላይ የተለያዩ ቀለማት ያሉዋቸው አዝራሮች ደርድራለች፡፡
“አንቺን ነው የማገባው!” ሲላት ደስታዋ ደመና ጠራርጐ እንደሚሸኝ ንፋስ የፊትዋን ገጽ ይገፋዋል፡፡ ጠይም ፊቷ ፀሐይ ብልጭ ይልበታል፡፡
ዛሬ ገና ሲለያዩ “አሁን ሁሉም ነገር  በቃ! አንቺን ተነጥቄማ አልኖርም!” አለ ለራሱ፡፡ ከዚህች ቀየ፣ ከዚህች ሠፈር መለያዬ ደረሰ፡፡ ዓባያ ሀይቅ ዳር ሄጄ ከብት ማሠማራቴ ፣ ከጓደኞቼ ጋር የነበረኝ ጨዋታ፣ የምወደው ወይፈን የመጋልም ግሳት፣ ሊያበቃ ነው…” ብሎ አይኖቹ እንባ አቀረሩ፡፡
ከዚህች ከሚኖርባት ላንፉሮ ተራራ ግርጌ ዓባያ ሀይቅ አለ፡፡ ያ ሀይቅ ደግሞ የእርሱና የጓደኞቹ የፌሽታ ቦታ ነው፡፡ ከብቶች እያገዱ፣ አንዳንዴም ፈረስና አህያ እየጋለቡ ይጫወታሉ፡፡ ከየቤታቸው ያመጡትን ቂጣና እንጀራ፣ በቡድን እየተሻሙ ይበላሉ፡፡ አንዳንዴም ከሀይቁ ዳር አልፎ አልፎ ካሉት ግራሮች ሥር ተቀምጠው ገበጣ ይጫወታሉ፡፡
እዚህ ደግሞ ጋራው ላይ ከፉንጐ ጋር ዓይን-ላይን፣ ልብ-ለልብ ይሠራረቃሉ፣ ዘፈንዋን ያዳምጣል። ጨለምለም ካለ ደግሞ አንገትዋ ሥር ይስማታል፡፡ አያቱን ቡና ልትጠራ ስትመጣ፣ ሰው ከሌለ እቅፍ ያደርጋታል፡፡ በእርሷ ምክንያት ሕይወት ደስ ይለዋል፡፡ ኑሮ ይጣፍጠዋል፡፡ አሁን ግን በቃ፣ ሞት ፊት ለፊቱ ቆሟል፡፡
“ጉ - ሌ.” ጠሩት አያቱ፡፡ ከተቀመጠበት ሜዳ መጣና ጎንበስ ብሎ ገባ፡፡ አባ ሲርመታ፣ ጋሽ አሰፋና ሌሎችም የጎረቤት ሰዎች አሉ፡፡
“በል ሰላም በል!” አሉት አያቱ፡፡
ሁሉንም በየተራ ሰላም አላቸው፡፡
“አንተ በተስኪያን አትሥምም!...” አሉት አባ ሲርመታ ቆጣ ብለው፡፡ አባ ሲርመታ ብዙ ጥርሶቻቸው ስለወለቁ ጉንጫቸው እየጎደጎደ፣ሲናገሩ አፋቸው ይኮላተፋል፡፡
አጎንብሶ ዝም አለ፡፡ ጋቢያቸውን ትከሻቸው ላይ አስተካከሉና፤ “ይህ‘ኮ የባልቻ አባነፍሶ ሀገር ነው፡፡ … አለማወቅህ እንጂ! … ጀግና የከተመበት የክርስቲያን ሀገር ነበር! ..” አሉና እንደመቆጨት አሉ፡፡
“ተወው እባክህ… ልቡን ሲገዛ ወደ ፈጣሪ ራሱ ይመጣል፡፡” አሉ ጋሽ አሰፋ፡፡ ጋሽ አሰፋ ቦላሌ አይታጠቁም፡፡ ጉልበቱ ላይ የተቆረጠ ቦላሌ  የመሰለ ነገር እስከ ባታቸው ነው የሚለብሱት፡፡
“በል ተቀመጥ!” አሉት፤ ተቀመጠ፡፡
“ዛሬ አንተ ልጅ ሁኔታህ ጥሩ አይደለም!” አሉ አያቱ፡፡
“ምንም አልሆንኩ!” ብሎ አጉተመተመ፡፡
“ከጎረመሥክ ሚስት እድርሃለሁ፡፡” ሲሉት እንደማፈር አለና አቀረቀረ፡፡
የቡና ቁርስ ተሰጥቶት ቡናውን ከጠጣ በኋላ ሀሳቡን ለመፈጸም ተነሳ፡፡ መጀመሪያ ከዓባይ ሀይቅ ከፍ ብሎ ወዳለው ኩሬ ሄደ፣ እዚያ ሲደርስ ፉንጎ ውሃዋን ቀድታ ማሰሮዋን እግርዋ ሥር አስደግፋ ተቀምጣለች፡፡ እንደደረሰ እጅዋን አንጠልጥሎ ወደ ዓባያ ወሰዳት፡፡
ትንፋሽ እስኪያጥራት እያጣደፈ አደረሳት፡፡
ዓባያ ደርሶ ግራና ቀኝ ሲያይ እረኞች ራቅ ብለው ግራር ዛፍ ስር ተኝተዋል፡፡ ጠረኑን የለመደው መጋል “እምቧዋ” አለ - ሲያየው፡፡ መልስ አልሰጠውም፤ ሆዱ ግን ባባ፡፡ አንገቱን ሲያሻሸው ዝቅ ብሎ ስሩ መግባት ለምዷል፡፡
 ኮቱን አውልቆ “ያዢልኝ” አላት ፉንጎን፡፡ ከዚያ ፈረሱ ላይ አስቀመጣት፡፡
“ጉሌ፤ - ካገኙን ይገድሉናል፡፡”
“እነማን?”
“እኔን ለማግባት የጠየቀኝ ልጅ ቤተሰቦች!”
“እኔ በሶ ጨብጫለሁ!”
“አሁን ወዴት ነው የምትወስደኝ?”
“ወደ ማረቆ”
“ማረቆ ወዴት ነው?”
“ተከተይኝ!”
ፊትዋን ነጠላ አከናነባት፡፡ እርሱም ጭንቅላቱ ላይ ጨርቅ ጠመጠመ፡፡ ዓባያን ዳርዳር ይዘው በገርቢ በር ገበያ በኩል ሜዳውን ይዘው በየፈረሶቻቸው ይጋልቡ ጀመር፡፡ “ጥሩ ሰንጋ ፈረሶች ናቸው፡፡” አላት፡፡ እሷ ግን ከቀልቧ አልነበረችም፡፡ መምሬ ካሣ ምን ይሉ ይሆን? እያለች ልቧ ይመታል። ጉሌን ግን ትወደዋለች፡፡
“ጉልዬ … መሸ!”
ከኪሱ እሸት በቆሎና ስልቅጥ የተጋገረ ቂጣ ሰጣትና በላች፡፡
“አይዞሽ!... እንደርሳለን…”
“ጅብ የለም?!” ጠየቀችው፡፡
“ይኑራ!”
ጅቡን የጠራችው ይመስል ወዲያው ድምፅ ተሰማ፡፡ ገና ባዶ ምድረበዳ ላይ ናቸው፤ የሰዎች መኖሪያ ሰፈር አልደረሱም፡፡ ደነገጠች፡፡
“የሚጮኸው ከሩቅ ነው!” አላት እንዳትፈራ፡፡
ሌላ ቅልጥ ያለ ጩኸት ድንገት ከፊታቸው ተሰማ፡፡
 “ም-ን-ድ-ነ-ው?” አለች፡፡
“ምንም የለም አትፍሪ… እሺ!”
ብዙ ፈረስ የያዙ ሰዎች ማረቆ መግቢያ አካባቢ ይተራመሳሉ፡፡
“ቁም! … ቁም!..ማ-ነ-ህ? ማነህ?” አሉ፡፡
“እንዲህ ጉድ ታደርጊኝ ልጄ!...እንዲህ ጉድ ትሰሪኝ!” መምሬ ካሳ ናቸው፡፡ ፉንጎ ሰማይ ምድሩ ዞረባት፡፡
ጉልላት ግን መሰናክል ሆኖ ፊቱ የተጋረጠበትን በድፍረት ተጋፍጦ ሽምጥ ጋለበ ወደ - ማረቆ፡፡
ጩኸቱ ቀለጠ፡፡
“ገደለው --- ገደለው!”
 “ያ-ሳ-ዝ-ና-ል! ቢላዋ ሰክቶበት ሄደ፡፡” ወደ ኋላ ቀረት ብላ የነበረችው ፉንጉ፤ በደመነብስ ያባትዋን ፈረስ ለቀም አድርጋ ጉልላትን ተከተለችው፡፡
“ጉ-ሌ!... ጉሌ!” ዘወር ብሎ አያት፡፡
ሁለቱ ፈረሶች ጩኸቱን ከኋላቸው አስቀርተው ወደፊት ሸመጠጡ፡፡
“በርቺ!” አላት፡፡ ሜዳውን ሽምጥ ጋለቡ፡፡ ጨረቃ ገና አልሳቀችም፤ክዋክብት ፊታቸውን በብርሃን አልታጠቡም፡፡ ሰቀቀንና ፍርሃት ልቦቻቸው ላይ እስክስታ እየመቱ ነው፡፡ ከበሮ መደለቃቸውን ቀጥለዋል፡፡
ድ-ን-ገ-ት “ጉ---ድ----ጓ----ድ!” አለ ጉልላት፡፡
ፉንጎ ዘወር ብላ ስታይ ጉሌ የለም፡፡ ፈረስዋን አዞረችው፡፡ ጉድጓዱ ውስጥ ድምጽ ሰማች፡፡ “ተ---በ---ላ---ሁ!” የሚል፡፡ ከፈረስዋ ወረደች፡፡…ፈረሱን ትታ ወደ ጉድጓዱ ዘለለች፡፡
የሲቃ ድምጽ….ተስተጋባ፡፡….  

Published in ጥበብ
Saturday, 18 July 2015 11:49

የኪነጥበብ ጥግ

 (ስለ ፊልም)
ይሄ ፊልም 31 ሚ.ዶላር ፈጅቷል፡፡ በዚህ ዓይነት ገንዘብ የሆነ አገር መውረር እችል ነበር፡፡
ክሊንት ኢስትውድ
ፀሐፊ መሆን ትፈልጋለህ? መፃፍ ጀምር፡፡ ፊልም ሰሪ መሆን ትፈልጋለህ? አሁኑኑ በስልክህ ምስሎችን መቅረፅ ጀምር፡፡
ማቲው ማክኮናሄይ
ፊልም የጦር ሜዳ ነው፡፡
ሳም ፉለር
ኮሜዲ ለመስራት የሚያስፈልገኝ፡- መናፈሻ፣ ፖሊስና ቆንጆ ልጃገረድ ብቻ ነው፡፡
ቻርሊ ቻፕሊን
መልዕክት ማስተላለፍ ከፈልግህ፣ ዌስተርን ዩኒየንን ሞክር፡፡
ፍራንክ ካፕራ
የፊልም መጨረሻ ሁልጊዜ የህይወት መጨረሻ ነው፡፡
ሳም ፔኪንፓህ
የምታየው የምታየው ፊልም በሲኒማ ቤት ውስጥ መቀመጥህን ማስረሳት አለበት፡፡
ሮማን ፖላንስኪ
እያንዳንዱ ዳይሬክተር በትንሹ 10 መጥፎ ፊልሞች አሉት፡፡
ሮበርት ሮድሪጉዝ
ፊልም ስትመለከት የዳይሬክተሩን የሃሳብ ሂደት ነው የምትመለከተው፡፡
ኦሊቨር ስቶን
እየተመፃደቅሁ አይደለም፤ ነገር ግን ፊልሞቼ ከ1ቢ. ዶላር በላይ ገቢ አስገኝተዋል፡፡
ስቲቭ ጉተንበርግ
እያንዳንዱ ድንቅ ፊልም ባየኸው ቁጥር አዲስ መምሰል አለበት፡፡
ፊልም ስቀርፅ እንዴት መቅረፅ እንዳለብኝ ፈፅሞ አላስብም፡፡ ዝም ብዬ ነው የምቀርፀው፡፡
ማይክል አንጄሎ አንቶኒዮ
ሰዎች ፊልም ት/ቤት ገብቼ እንደሆነ ሲጠይቁኝ፤ “በፍፁም አልገባሁም፤ እኔ የገባሁት ፊልሞች ውስጥ ነው” እላቸዋለሁ።
ኳንቲን ታራንቲኖ
በተለይ በአስፈሪ ፊልሞች ወስጥ ለገፀባህሪያቱ ካልተጠነቀቅህ፣ ተመልካቾችህን እንደምታጣ ይሰማኛል፡፡ ማንም ጉዳዬ አይለውም፡፡ እናም ፊልሙ ሰዎች ሲገደሉ የማየት ሂደት ይሆናል፡፡
ድሪው ጎዳርድ
ከፊልሞች ጋር ምርጥ ተሞክሮ ያገኘሁት ምን ዓይነት ፊልሞችን ማየት እንዳለብኝ በማላውቅ ጊዜ ነበር፡፡
ዣን ፓል ጋውልቲር
ህይወቴን ጨርሶ ከፊልሞች ውጭ ላስታውስ አልችልም፡፡
ኢሌ ፋኒንግ
እንደ ዕድል ሆኖ ፈፅሞ ዝነኛ ለመሆን ፈልጌ አላውቅም፤ ፍላጐቴ ፊልም መስራት ብቻ ነበር።
ሴዝ ሮጀን

Published in ጥበብ

 ማለዳ የጀመረው ካፊያ ማቆሚያ ያለው አይመስልም፡፡ ዕለቱ የታዋቂው ወግ ፀሐፊ መስፍን ሀብተማርያምን አንደኛ ሙት ዓመት መታሰቢያ ለመዘከር በ“የጠፉትን ፈላጊ ፕሮሞሽን” አስተባባሪነት ከጊዮርጊስ ተነስቶ በፒያሣ አትክልት ተራ በኩል አልፎ፣ መርካቶ በመግባት ክፍለ ሀገር አውቶብስ ተራ ጋ የሚጠናቀቅ የእግር ጉዞ የተካሄደበት ነበር። በፕሮግራሙም  ከተለያዩ ተቋማት የተጋበዙ 30 ሰዎች ተሳትፈዋል፡፡
የባለፈው ማክሰኞ ካፊያና ቅዝቃዜ ከቤት መውጣት ባያስመኝም ባልተለመደ መልኩ የተጠሩት ተጋባዦች ሁሉ ጊዮርጊስ አደባባይ ተገኝተዋል፡፡ እንደውም ከጥሪው ሰዓት ቀድሞ እንጂ ዘግይቶ የደረሰ አንድም ሰው አልነበረም፡፡ የሚበዛው ሰው ዣንጥላ ይዟል፡፡ በአንገታቸው ዙሪያ ስካርቭ የጠመጠሙም ጥቂት አይደሉም፡፡ ባለ ኮፊያ ሻማ ጃኬትና ካፖርት የደረቡም ነበሩ፡፡
“የጠፉትን ፈላጊ ፕሮሞሽን” መስራችና የዝግጅቱ አስተባባሪ ወጣት ፈለቀ ጋሻው የጠራቸው እንግዶች በሙሉ ሰዓታቸውን አክብረው በመገኘታቸው የተሰማውን ደስታ ቃላት አውጥቶ ማመስገን ከመጀመሩም አስቀድሞ ፊቱ ላይ ይነበብ ነበር፡፡
“በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ብዙዎቻችን እንተዋወቃለን ብዬ ስለምገምት እርስ በእርስ በማስተዋወቅ ጊዜያችሁን አላጠፋም፡፡ በጉዟችን  ላይ ገለፃ የሚያደርጉልን ሰዎች ተመርጠዋል፡፡ የማንተዋወቅ ካለን በዚህ አጋጣሚ እንተዋወቃለን፡፡ ይህንን ዝግጅት ለማሰናዳት ምክንያት የሆነኝ የደራሲና ወግ ፀሐፊው ጋሽ መስፍን ሀብተማርያምን መዘከሪያ ማዘጋጀት ቢሆንም የታዋቂው ደራሲያችን መዘከሪያ መድረክ ላይ ሌሎችንም ለማስታወስ ስለፈለኩ፤ ሀሳቡን ያቀረብኩላቸው አካላትም ስለተስማሙበት ነው ዛሬ በጠዋት እዚህ የተሰባሰብነው፡፡”
የዕለቱ መርሐ ግብር ከጥንታዊት ኢትዮጵያ አርበኞች ማህበር በመጡት አባት ገለፃ ነበር የጀመረው፡፡ “ታላላቅ ታሪካዊ ክንውኖች የተፈፀመበት አደባባይ ላይ ነው የምንገኘው። ሐውልታቸው በዚህ አደባባይ ስለቆመው አፄ ምኒልክ ካልነገርኳችሁ ብዬ አላደክማችሁም፡፡ አፄ ኃይለሥላሴ በአራዳ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ዘውድ መድፋታቸውን መንገርም በዚህ ማለዳ እላያችሁ ላይ የተከመረውን ብርድ አያራግፍላችሁም፡፡
“ባይሆን ልባችሁን የሚያሞቅ፣ ስሜታችሁን አነሳስቶ የሚያስገርም አንድ ሁለት ጉዳይ ልንገራችሁ። የአድዋ ጦርነት ድል 7ኛ ዓመት በ1895 ዓ.ም በዚህ አደባባይ ሲከበር በበዓሉ እንዲታደም ለተጠራው 60 ሺህ ህዝብ ማስተናገጃ 8 ሺህ በሬ ታርዶ ነበር፡፡ ዛሬም የዚህ መንደር ታዋቂ ንግድ የሉኳንዳ ቤት ነው፡፡ በከተማችን ከዓመቱ መግቢያ እስከ ማጠናቀቂያ ሥጋ ተፈልጎ የማይታጣበት ቦታ ነው፡፡
“ሌላው በ1950ዎቹ በእንግሊዝ አገር ግር የተሰኘሁበት ሚስጢር፤ እግዚአብሔር ዕድሜ ሰጥቶኝ፤ አራዳ ጊዮርጊስ ከርሰ ምድር ውስጥ መዘርጋት ስለቻለው ጉዳይ ነው የምነግራችሁ። በአውሮፓ የአገር መሳቂያ የሆንኩት ‹በባቡር ና› ወደ ተባልኩበት ቦታ ለመሄድ አስፋልት ላይ ቆሜ፣ በግራ ቀኜ ሐዲድ እየፈለግሁ፣ ባቡር ጣቢያው የት እንደሆነ እጠይቅ የነበረው፤ ከቆምኩበት ወለል ስር የሚርመሰመሰው ትራንስፖርት መግቢያ አንዲት ትንሽ ደረጃ ማስተዋል ባለመቻሌ ነበር፡፡ ያ የሰው ልጆች ጥበብ እዚሁ በአገሬ ተሰርቶ አየሁ፤ ድንቅ ነው፡፡”
የአርበኛው አባት ገለፃ ሲያበቃ ወደተዘጋጀልን አውቶብስ ገባን፡፡ ለአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ሥራ አጥሩ የተደፈረው አሮጌው ማዘጋጃ ቤት፣ ቀሪውን አድሶ መልክ የሚያስይዝለት ማጣቱን ከጉዟችን ተሳታፊዎች ሁለቱ ሲነጋገሩበት ሰማሁ፡፡ ማነፃፀሪያቸው አዲሱ የማዘጋጃ ቤት ህንፃ አጥርም ለልማቱ ፈርሶ የነበረ ቢሆንም፣ ስራው ካለቀ በኋላ ተመልሶ መገንባቱን እያመሳከሩ ነበር የሚወያዩት፡፡
የዝግጅቱ አስተባባሪ በጭብጨባ የአውቶብሱን ተሳፋሪዎች ቀልብ ወደራሱ ከሳበ በኋላ ከዩኒቨርሲቲ የተጋበዘውን ወጣት የታሪክ ምሁር ማንነት አስተዋወቀን፡፡ አቶ በቀለ ለማ ይባላል፡፡ አቶ በቀለ የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ለልማት የተነሳ ዕለት በቦታው እንደነበረና ሐውልቱን ወደነበረበት ለመመለስ ምን ሂደት ላይ እንዳለ ገለፃ እንዲሰጠን ተጋበዘ፡፡
“በብዙ መድረኮች ‹ታላቅ ሰው ከተናገረ በኋላ እኔ ታናሻቸው መጋበዜ ተገቢ አይደለም› እያሉ አክብሮታቸውን በትህነትና የሚገልፁ ሰዎች ያጋጥሙኛል፡፡ እኔ ግን እንኳንም ከትልቅ ሰው በኋላ የመናገር ዕድል አገኘሁ ብያለሁ፡፡ ምክንያቱም የምታውቁትን ነገር በመስበክ እንዳላሰለቻችሁ ከአባት አርበኛው ገለፃ ትምህርት አግኝቻለሁ፡፡
“ስለዚህ የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ሚያዚያ 25 ቀን 2005 ዓ.ም ከዚህ ቦታ መነሳቱን፣ ከአንድ ዓመት በኋላ ወደነበረበት ይመለሳል የሚል ቃል መገባቱን፣ ከዛሬ ነገ ወደ ቦታው ይመለሳል እየተባለ በተደጋጋሚ በመነገር ላይ መሆኑን ልንገራችሁ ብል ጆሮ አትሰጡኝም፤ ደጋግማችሁ ሰምታችሁታልና። ጆራችሁን ብቻ ሳይሆን ዓይናችሁን የሚስብ ነገር ልንገራችሁ፡፡ ፋሽስቱ በአቡነ ጴጥሮስ ላይ የሞት ፍርድ የፈረደበት ቤት የት እንደሚገኝ ስንቶቻችን እናውቃለን?” ወጣቱ የታሪክ ምሁር የብዙዎቻችንን ቀልብ መሳብ ቻለ፡፡ ከአውቶብሱ በስተግራ ጂማ ባር ያለበትን ብሎክ ቤቶች እያሳየን፣ የአቡነ ጴጥሮስ የሞት ፍርድ ከነዚያ ቤቶች በአንዱ ክፍል ውስጥ መወሰኑን አሳወቀን፡፡
ቀድሞ የኢትዮጵያ ሬዲዮ አገልግሎት ማሰራጫ የነበረውንና አሁን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ  የጋዜጠኞች ማሰልጠኛ የሆነውን ግቢ እንዳለፍን፣ ከስፖርት ኮሚሽን የመጡት አቶ በላቸው ተካ ቀጣዩን ገለፃ እንዲደርጉልን ከሹፌሩ ጀርባና ከተሳፋሪዎች ፊት ለፊት ያለው መድረክ ተሰጣቸው፡፡
“በቀድሞ ዘመን የጊዮርጊስ ፒያሣ አንዱ መለያቸው የእግር ኳስ ጨዋታና የብስኪሌት ግልቢያ ውድድሮች በብዛት የሚካሄድባቸው መሆኑ ነው፡፡ ወደዚህ አካባቢ የሚመጡ ሰዎች ጊዜው ስንት ላይ እንደደረሰ የሚያውቁት ከአትክልት ተራ ነባር ቤቶች በአንዱ ላይ በተሰቀለው የአደባባይ ሰዓት ነበር፡፡ የአዲስ አበባ ህዝብ ከሰዓት ጋር ያለው እውቂያ ምን እንደሚመስል ታሪክ ጽፎ የሚያሳትም ካለ፣ በልማት ምክንያት ከፒያሣ አትክልት ተራ አሮጌ ህንፃዎች ጋር የተወገደውን ሰዓት ታሪክና ውለታ እንዲያካትቱ አደራ እላለሁ፡፡ ለስፖርተኞች ሰዓትና ጊዜ ምን ማለት እንደሆነ፤ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ አንዲት ሰከንድን በመጣል የሚሊዮን ዶላር ሽልማት ሊያጣና ለሽንፈት ሊዳረግ እንደሚችል የነገረንን ምክር መቼም አንረሳውም ብዬ እገምታለሁ፡፡”
ከአውቶብሱ ወርደን ፒያሣ አትክልት ተራን ዞረን እንድንጎበኝ ተደረገ፡፡ በአካባቢው ወደ ዘመናዊ ሕንፃ ለመግባት የሚታትር ንግድና የጎዳና ግብይት ተፋጥጠው አየን? ማን እንደሚያሸንፍ ለማናችንም ግልጽ ነበር፡፡ ይህ እውነታ ወደ መርካቶ ስንገባ በስፋት እንደሚገጥመን እየታሰበን ወደ አውቶብሳችን ተመለስን፡፡
ቀጣዩ ገለፃ አድራጊ ከንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የመጡት አቶ በርናባስ ሄኖክ ነበሩ። “እኔም ብዙ አልተነገረለትም ብዬ የገመትኩትን ታሪክ ነው የምነግራችሁ” ብለው ገለፃቸውን ጀመሩ፡፡ “አሁን አለ በጅምላ የመርካቶ ቅርንጫፍ የተከፈተበት የቀድሞ ጅንአድ ግቢ የመጀመሪያው ባለቤት ቤስ የሚባሉ የውጭ አገር ባለሀብት ነበሩ። ባለሀብቱ የኢትዮ-ጅቡቲ የምድር ባቡር ድርጅትን ለመግዛት ለመንግሥታቱ ጥያቄ አቅርበው ነበር ይባላል፡፡ ኩባንያው ለባለሀብቱ ተሸጦላቸው ቢሆን ኖሮ፣ የባቡር ትራንስፖርት ዕድገታችን የት ይደርስ ነበር ይሆን? ወደፊትም ዘርፉ ለግል ባለሀብት ቢሸጥ፤ ጠቀሜታና ጉዳቱ ምን እንደሆነ መነጋገሪ መድረክ ቢፈጠር ጥሩ ነው የሚል አቋም አለኝ፡፡ ይህ አቋም እራሴን እንጂ የመጣሁትን ተቋም አይወክልም፡፡”
መርካቶ ውስጥም ዘመናዊውና ባህላዊው ንግድና ነጋዴዎች ተጎራብተው፣ ተቃቅፈው፣ ተደጋግፈው … ሲያስኬዱት አየን፡፡ ፈርሶ የተገነባው፣ በመገንባት ላይ ያለው፣ የሚፈርሰውም ብዙ ነው፡፡ ከባንኮች ማህበር የመጡት አቶ ሀብታሙ ልክየለው፤ መርካቶ ውስጥ በልማት ምክንያት ከፈረሱት ቤቶች ጋር በተያያዘ የአገሪቱን ዕድገት እንዲያብራሩልን በዝግጅቱ አስተባባሪ ተጋብዘው ፊት ለፊታችን ቆሙ፡፡
“ዛሬ በዚህ ጉዞ ሁላችንም የተማርነው ነገር የሚታወቅና ተደጋግሞ የተነገረ ታሪክ ካልነገርኳችሁ ብሎ በአድማጭ ጆሮና ጊዜ ላይ መቀለድ ተገቢ አለመሆኑን ነው፡፡ የአገሪቱ ‹የፋይናንስ ተቋማት መንደር› በብሄራዊ ባንክ ዙሪያ እንዲገነቡ መጠነ ሰፊ እቅድ ተነድፎ ተግባራዊ ሥራዎች ከተጀመሩ ሰነባብቷል፡፡ የፋይናንሱ ዘርፍ ወደዚህ ደረጃ ያደገው በትናንሽ ባንክ ቤቶች ከመስራት ተነስቶ ነው፡፡ መርካቶ ውስጥ በልማት ምክንያት የፈረሰውና ለገበያዋ የመጀመሪያ የፋይናንስ ተቋም ሆኖ ያገለገለው ‹ቁጭራ ባንክ ቤት› አንዱ ማሳያ ነው፡፡”
የጉዞው ማጠናቀቂያ እንዲሆን ወደታቀደውና ለዝግጅቱ መሰናዳት ምክንያት ወደሆነው አዲስ ከተማ መሰናዶ ትምርት ቤት አካባቢ ደርሰናል፡፡ መርካቶ ውስጥ ከሰባት ፎቅ በላይ ካላቸው በጣት የሚቆጠሩ ህንፃዎች አንዱ እዚህ አካባቢ በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡ የህንፃው ባለቤት ንግድ ባንክ ሲሆን፤ ቦታው ላይ በቀድሞ ጊዜ “አምባሳደር ሆቴል” ተብሎ የሚጠራ ባለ ሁለት ፎቅ ህንፃ እንደነበረበት “የጠፉትን ፈላጊ ፕሮሞሽን” መሥራችና የዕለቱ ፕሮግራም አዘጋጅ ገለፃ አደረገልን፡፡
በልማት ምክንያት የፈረሰው የአምባሳደር ሆቴል ህንፃ በኢትዮጵያ ስነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ መቼም ቢሆን ሊረሳ የማይችል የወግ ጽሑፍ እንዲፃፍ ምክንያት የሆነ የግድግዳ ላይ ሥዕል ይገኝበት እንደነበርም አብራራልን፡፡ በሆቴሉ ቡና ቤት መጽሔትና ጋዜጦች በብዛት ይነበቡ እንደነበርና ሆቴሉ ለንባብ መዳበር ባለውለታ እንደነበረም ተወሳ፡፡
ከዚህ ሆቴልና ደንበኞች አንዱ የነበረው ደራሲና ወግ ፀሐፊ መስፍን ሀብተማርያም “የቡና ቤት ሥዕሎች” በሚል ርዕስ ስለፃፈው ወግና ለሥዕሉ መነሻ ስለሆነው ሥዕል እንዲያስረዱ በዘርፉ ሁለገብ ሐያሲ ናቸው የተባሉት ወ/ሮ አቻምየለሽ ዓለሙ ተጋበዙ፡፡
“ባህላዊው የኢትዮጵያ ሥዕል ወደ ዘመናዊ የአሳሳል ዘዴ እንዴት እንደተሻገረ ጥናትና ምርምር ቢደረግ የቡና ቤት ሥዕል ሰዓሊያን ድልድይ ሆነው ይገኛሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡ የቡና ቤት ሥዕሎችን እንደሚገባው አጥንተናቸዋል ወይ? በሻይ ቤቶች፣ ጠጅ ቤቶች፣ ሆቴሎች ግድግዳ ላይ ተስለው የነበሩት ሥዕሎች የምንማርባቸው ብዙ ቁምነገር ነበራቸው። ጋሽ መስፍን ሀብተማርያም ባየበት መልኩና ትንታኔ ባቀረበበት ዘዴ በስፋት አልተጠኑም የሚል የግል እምነት አለኝ፡፡ ከነባር ቤቶቹ ጋር ሥዕሎቹም አብረው እየጠፉ ነው፡፡
በዚህ አጋጣሚ የቡና ቤት ሥዕሎችን ይዘትና ቅርጽ ከቻልን፣ እንደ ጋሽ መስፍን በጽሑፍ በመግለጽ፣ ካልቻልን ፎቶግራፍ በማንሳት ለታሪክ እንዲቀሩ ብናደርግ የሚል መልዕክት አለኝ። ደራሲው በሌለበት፣ ሥዕሉም በማይገኝበት በዚህ ቦታ ዛሬ መሰባሰብ የቻልነው በነበረ እውነታ ላይ የተሰራ ሥራና ሰሪውንም ለመዘከር ነው፡፡ ስለዚህ አዲስ ነገር ስንጨምር ነባሩ ሥራ የህዝብና የአገር ታሪክ አካል እንዲሆን አስበንና አቅደን እንስራ፡፡”

Published in ጥበብ
Page 5 of 17