በምርጫ ማግስት እየተፈፀመ ያለው ወከባና
እንግልት እንዲቆም የሚጠይቅ ነው ተብሏል

     የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ በአባላቱና መድረክን በመረጡ ዜጎች ላይ እየደረሰ ነው ያለው ወከባና እንግልት በአስቸኳይ እንዲቆም የሚጠይቅ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ መፃፉን አስታወቀ፡፡ ከምርጫው በፊት በሃገራዊ ጉዳይ ላይ ለመወያየት የሚጠይቅ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገብቶ ምላሽ እንደተነፈገው ለአዲስ አድማስ የገለፁት የመድረክ ሊቀመንበር ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ፤ የአሁኑ ደብዳቤ በአባላቱና መድረክን በመረጡ ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን ወከባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ
ባላቸው ኃላፊነት በአስቸኳይ እንዲያስቆሙ የሚጠይቅ ነው ብለዋል፡፡ በምርጫው ማግስት በኦሮሚያ ክልል አቶ ጊደሳ ጨመዳና አቶ ገቡ ጥቤሶ የተባሉ የመድረኩ አባሎች መገደላቸውንና በክልሉ በርካታ አባላት በየፖሊስ ጣቢያውና በየወህኒ ቤቱ መታጎራቸውን፣ በትግራይም የአረና መድረክ አመራር አቶ ታደሰ አብርሃ እንዲሁም በደቡብ የመድረኩ የምርጫ ታዛዚ የነበሩት አቶ ብርሃኔ ኤረቦ መገደላቸውን የጠቀሰው የመድረክ ደብዳቤ፤ በርካታ አባላትና ደጋፊዎች በየክልሎቹ በእስር ላይ እንደሚገኙ፣ የመንግስት ሰራተኛ የሆኑ አባሎችም ደሞዛቸው እየታገደና ከስራ እየተባረሩ መሆኑን ይገልፃል፡፡ በብዙ አካባቢዎችም በመድረኩ የምርጫ ተወካዮች ላይ ድብደባ፣ የግድያ ሙከራና ከቤት ንብረት የማፈናቀል እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን ደብዳቤው ጠቁሟል፡፡ በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች “ኢህአዴግን ለምን አልመረጣችሁም” በሚል በዜጎች ላይ ከፍተኛ ወከባ እየተፈፀመ ነው ያሉት ፕ/ር በየነ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ባላቸው ከፍተኛ ሃገራዊ ኃላፊነት ድርጊቱን እንዲያስቆሙ በመድረኩ ስም ጠይቀዋል፡፡  “የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ
ሰኔ 15 ይፋ ያደረገውን የምርጫ ውጤት ሰፊው ህዝብ አልተቀበለውም” የሚለው ደብዳቤው፤ መድረክን በመረጡ ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን ወከባና እንግልት ለቦርዱ በተደጋጋሚ በደብዳቤ ቢያሳውቁም ቢሞከርም ቦርዱ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ እንዳለፈው ጠቁሟል፡፡ መድረክ ከምርጫው በፊት ከመንግስት ጋር መወያየት እንደሚፈልግ ጠቅሶ ጥር 7 ቀን 2007 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ የጠየቀው ቀጠሮ በቸልታ መታለፉ፣ ከምርጫው በኋላ ለተከሰቱት ችግሮች አስተዋፅኦ ማበርከቱን ፕ/ር በየነ ተናግረዋል፡፡  

Published in ዜና

     ባለፈው ግንቦት በተካሄደው 5ኛው አገራዊ  ምርጫ ሰማያዊ ፓርቲን በመወከል ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በደብረማርቆስ ከተማ ተወዳድሮ የነበረውን ወጣት ሳሙኤል አወቀን ገድሏል በተባለው ተከሳሽ ላይ ፍርድ ቤት የ19 ዓመት ፅኑ እስራት ፈረደበት፡፡ የምሥራቅ ጐጃም ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ከትናንት በስቲያ በሰጠው ውሳኔ፣ ሟች ሳሙኤል አወቀን በመደብደብ ለህልፈት ዳርጐታል በሚል ወንጀል ክስ በተመሰረተበት ተቀበል ውዱ ላይ የአስራ ዘጠኝ ዓመት ፅኑ እስራት ፈርዶበታል፡፡ ተከሳሹ ገንዘብ ወስዶ አስቀርቶብኛል በሚል ምክንያት ከሟች ጋር ግጭት መፍጠሩንና በዚህ ምክንያትም ከግብረአበሩ ጋር በመሆን ሟችን ደብድቦ ለሞት እንዳበቃው የአቃቤ ህግ ክስ ያመለክታል፡፡ ለወንጀሉ ተባባሪ የሆነው ተጠርጣሪ እስከአሁን ድረስ አለመያዙም ተጠቁሟል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ የፍ/ቤቱን ውሳኔ፤ በወንጀሉ ውስጥ ተሣትፏል የተባለው ተባባሪ ባልተያዘበት ሁኔታ በአስራ ሰባት ቀናት ውስጥ በተሰጠው የፍርድ ውሣኔ ቅሬታ እንዳለው ገልጿል፡፡ በአዲስ አበባ ለወራት በእስር ተይዘው የሚማቅቁ የፓርቲው አባላት እስከአሁን ምንም አይነት ውሣኔ እንዳልተሰጣቸው ፓርቲው ጠቁሟል፡፡

Published in ዜና

      በቅርቡ ኢትዮጵያን ይጐበኛሉ ተብለው የሚጠበቁት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ መንግስትን ብቻ ሳይሆን እኛንም ያነጋግሩን ሲሉ ሶስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለአሜሪካ ኤምባሲ ባስገቡት ደብዳቤ መጠየቃቸውን ገለፁ፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል የሆኑት የኢትዮጵያውያን ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ)፣ የኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) እና የምክር ቤቱ አባል ያልሆነው የመላ ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ትናንት ለአሜሪካ ኢምባሲ ባስገቡት ደብዳቤ፤ ኦባማ
ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ አይቀር እኛንም በሰብአዊ መብቶችና በዲሞክራሲ ጉዳይ ላይ ያወያዩን ብለዋል፡፡
የኢዴፓ ስራ አመራር አባል አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ የምርጫ ውጤቱ በአንድ ፓርቲና አጋሮቹ ጠቅላይነት በተደመደመበት ሁኔታ ፕሬዚዳንቱ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት
እንዴት እንደወሰኑ እንጠይቃቸዋለን ብለዋል፡፡ “ከምርጫ 2007 በፊትም ሆነ በኋላ በአገሪቱ የሚፈፀመው የሰብአዊ መብት ጥሰት እየሰፋ ነው የሄደው” ያሉት አቶ ዋሲሁን፣ በዚህ ጉዳይ ላይ የአሜሪካ አረዳድ እንዴት ነው? የሚለውን  እንጠይቃቸዋለን፣ በጉዳዩ ላይም ከፕሬዚዳንቱ ጋር በሚገባ መወያየት እንፈልጋለን ብለዋል፡፡
አሜሪካ ለዲሞክራሲ ጠበቃ ነኝ የምትል ሃገር እንደመሆኗ በኢትዮጵያ የመድብለ ፓርቲ ስርአትና ዲሞክራሲ ያለበትን ሁኔታ በተመለከተ የአሜሪካ መንግስት እንዴት ነው እየተረዳ ያለው የሚለውንም ከፕሬዝዳንቱ ጋር ለመነጋገር እንደሚፈልጉ አቶ ዋሲሁን ገልፀዋል፡፡ በሌላ በኩል አጠቃላይ የምርጫውን ሁኔታ በተመለከተ ሶስቱ ፓርቲዎች በጋራ በመሆን የፊታችን ሰኞ በራስ ሆቴል መግለጫ እንደሚሠጡ የጠቆሙት አቶ ዋሲሁን፤  ፓርቲዎቹ የምርጫ ውጤቱን እንደማይቀበሉ ከዚህ ቀደም በተናጥል መግለፃቸውን አስታውሰው አሁንም በጋራ ከተለያዩ መመዘኛዎች አንፃር የምርጫውን ውጤት እንደማይቀበሉ ድምፃቸውን ያሰማሉ ብለዋል፡፡
ኢዴፓ፣ ኢራፓ እና መኢአድ ምርጫው ከመካሄዱ ቀደም ብሎ በሚያግባቡ ጉዳዮች ላይ በጋራ ሲሠሩ መቆየታቸውን ያስታወሱት አቶ ዋሲሁን፤ አሁንም በጋራ በሚያግባባቸው ጉዳዮች ላይ መስራታቸውን ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡ 

Published in ዜና
Page 17 of 17