ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፊልም ባለቤቶች ፈቃድ ውጭ በየድረ-ገፃቸው የኢትዮጵያ ፊልሞችን በማሰራጨት ህገወጥ ገቢ የሚሰበስቡ ወገኖችን የሚያወግዝና ፊልሞቹ የተጋረጠባቸውን ፈተና የሚያሳይ ዘጋቢ ፊልም፤ በዮናታን አበራ አድቨርታይዚንግ የተዘጋጀ ሲሆን የፊታችን ሰኞ በድሪም ላይነር ኢንተርናሽናል ሆቴል ከቀኑ 10፡30 ጀምሮ ይመረቃል ተብሏል፡፡  በአማርኛ ፊልሞች ላይ እየተሰራ ያለው ወንጀል የጋራ ጩኸት ስለሚፈልግ በዘጋቢ ፊልሙ ላይ የተለያዩ የፊልም ባለሙያዎች እንደተሳተፉበት ዮናታን አበራ አድቨርታይዚንግ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉ የድረ ገፅ ባለቤቶች፣ በፊልሙ ላይ እየሰሩ ያሉት ስራ ህገ-ወጥና የአማርኛ ፊልሞችን ከጨዋታ የሚያስወጣ በመሆኑ፣ ድርጊቱን ለማስቆም የተሰራውን ፊልም ለማሰራጨትና ግንዛቤ ለመፍጠር ከሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ የጠየቀው ድርጅቱ፤ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት እና ከኢትዮጵያ ኦዲዮ ቪዥዋል አሳታሚዎች ማህበር የድጋፍ ደብዳቤ ተሰጥቶታል፡፡ በዘጋቡ ፊልሙ ምረቃ ላይ በኪነ-ጥበብ ሥራ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች፣ የሚመለከታቸው ተቋማትና የመንግስት ባለስልጣናት ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል፡፡

በኢትዮ ፊልም ኃ/የተ/የግ/ማህበር አስተባባሪነትና ባለቤትነት የሚዘጋጀው “ጉማ ፊልም ሽልማት” የዘንድሮ ፊልሞችን በሽልማት ውድድሩ ለማካተት ምዝገባ መጀመሩን አስታወቀ፡፡ ለሁለተኛው ዙር የሚወዳደሩ የአምና ፊልሞችን ከመጋቢት 29 እስከ ሚያዚያ 3 በጣይቱ ሆቴል መዝግቦ ማጠናቀቁን የገለፀው ኢትዮ ፊልም፤ በሁለተኛው ዙር ውድድር የዘንድሮዎቹን ለማካተት ከሐምሌ 9 እስከ 16 በጣይቱ ሆቴል ምዝገባ እንደሚያካሂድና ለመመዝገብ ፍላጎት ያላቸው ፊልሞች እንዲመዘገቡ ጥሪ አቅርቧል፡፡ ምዝገባው ከቅዳሜ ከሰዓትና ከእሁድ በስተቀር በስራ ቀናት የሚካሄድ መሆኑንም ድርጅቱ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

በኢትዮ ፊልም ኃ/የተ/የግ/ማህበር አስተባባሪነትና ባለቤትነት የሚዘጋጀው “ጉማ ፊልም ሽልማት” የዘንድሮ ፊልሞችን በሽልማት ውድድሩ ለማካተት ምዝገባ መጀመሩን አስታወቀ፡፡ ለሁለተኛው ዙር የሚወዳደሩ የአምና ፊልሞችን ከመጋቢት 29 እስከ ሚያዚያ 3 በጣይቱ ሆቴል መዝግቦ ማጠናቀቁን የገለፀው ኢትዮ ፊልም፤ በሁለተኛው ዙር ውድድር የዘንድሮዎቹን ለማካተት ከሐምሌ 9 እስከ 16 በጣይቱ ሆቴል ምዝገባ እንደሚያካሂድና ለመመዝገብ ፍላጎት ያላቸው ፊልሞች እንዲመዘገቡ ጥሪ አቅርቧል፡፡ ምዝገባው ከቅዳሜ ከሰዓትና ከእሁድ በስተቀር በስራ ቀናት የሚካሄድ መሆኑንም ድርጅቱ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

ተቀማጭነቱን በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ያደረገው “ጣይቱ የባህል ማዕከል” በመጪው አርብ “ውሳኔ” የተሰኘ የስነ-ፅሁፍ ምሽት በአዲስ አበባ እንደሚያካሂድ የማዕከሉ የኢትዮጵያ ተወካዮች አስታወቁ፡፡
“ጣይቱ የባህል ማዕከል” ላለፉት 13 ዓመታት በአሜሪካና በአውሮፓ የኢትዮጵያን የኪነ-ጥበብ ስራዎች ሲያስተዋውቅና ሲያበረታታ እንደቆየ የገለፁት ተወካዮቹ፤ በመጪው አርብ ከቀኑ 10 ሰዓት ጀምሮ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ-መፅሀፍት ኤጀንሲ አዳራሽ ደማቅ የስነ-ፅሁፍ ምሽት እንደሚያካሂድ ተናግረዋል፡፡
በዝግጅቱ ላይ ግጥሞች፣ ወጎች እና መነባንብ የሚቀርቡ ሲሆን በርካታ ደራሲያን፣ ገጣሚያንና ጥሪ የተደረገላቸው የሥነጽሑፍ ቤተሰቦች እንደሚታደሙ ታውቋል፡፡

በአግዮስ ምትኩ የተደረሰውና “የአደራ መክሊት” የሚል ርዕስ የተሰጠው ትውፊታዊ ልብ-ወለድ መፅሀፍ ሰሞኑን በገበያ ላይ ውሏል፡፡ ባህላዊ መሰረት ያለው ትውፊዊ ልብ-ወለድ መፅሀፉ፤ ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ ስለመጣ አንድ ጥሩ መንፈስ ስላለው የአደራ መስቀል የሚተርክ ሲሆን መስቀሉ በተለያየ መልኩ ህይወት ባስተሳሰራቸው ገፀ-ባህሪያት ውስጥ መተላለፉ ሲቆም ስለሚገጥሙት ተግዳሮቶች ይዘረዝራል፡፡
በ60 ምዕራፎችና በ265 ገፆች የተመጠነው መፅሀፉ፤ በሊትማን መፅሀፍ መደብር አከፋፋይነት በ69 ብር ከ95 ሳንቲም እየተሸጠ ነው፡፡

ሳሙኤል ጆንሰን “The chief glory of every people a rises from its authors” ይላል። (የአንድ ህዝብ ደማቅ ስምና ታሪክ ከወለዳቸው ፀሐፍትና ደራስያን ጭምር ይፈልቃል እንደማለት ነው) እውነት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የአንድ ደራሲ የሕይወት ታሪክም የአንድ አገርና ሕዝብ ታሪክም ሲሆን አስተውለናል፡፡ የቅዱስ ያሬድ፣ የአባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ እና የመሳሰሉት ለውስጣችን ታላቅ ኃይል የሚሰጠን የፈጠራ ስራቸው ብቻ ሳይሆን የዚህች ሀገር መሰረት የሆነው የአኗኗር ዘይቤና ፈሊጣቸው ጭምር ነው፡፡
ፑሽኪን ለሩሲያ፣ ብረሽት ለጀርመን፣ ባልዛክ ለፈረንሳይ፣ ሼክስፒር ለእንግሊዝ፣ ሔሚንግዌይ ለአሜሪካ ሕዝብ የታሪኮቻቸው ምንጮች ናቸው፡፡
እነኚህ ደራሲያንና ሌሎችም ሁሉ በፈጠራቸው የሂደት ወቅት አድሏዊ ሆነው አያውቁም፡፡ ሂሳዊ የማይሆኑትና አልፎ አልፎ ሚዛናቸው የሚዛባው መፍረድ ሲጀምሩ ወይም ፍርድ ሲሰጡ ነው፡፡ ታድያ እነዚህን ሁለት የሥነ ጽሑፍ ምሰሶዎች ጠብቀው የተፃፉ ሥራዎችን ሲያስነብበን የኖረን አንድ የጥበብ ሰው አጥተናል፡፡
ሀገራችንና የጥበብ ወዳጆች የሆንን ሁሉ አንድን ዘርፈ ብዙ የጥበብ ሰው አጥተናል፡፡
ሀገራችን ባለቅኔ፣ ተርጓሚና ትሁት መምህር የሆነውን ልጇን አጥታለች፡፡
ከሁሉም ከሁሉም ታላቁን የወግ አባት አጥተናል፡፡ ወግ ለመቀመር የተፈጥሮ ችሎታውን ከዘመናዊ ትምህርት ጋር አጣምሮ የተካነን ሸጋ ደራሲ አጥተናል፡፡ ባሻው ዘውግ አሳምሮ መፃፍ የሚችል ደመና - ገላጭ ትንሽ ፈጣሪ አጥተናል፡፡
ታላቁ የወግ አባት መስፍን ሀብተማርያም ተለይቶናል፡፡
መስፍን ሀ/ማርያም የወግን ምንነት ያስተማረን ብቻ ሳይሆን በተለይ የርዕዮትንና የአብዮትን ዜማ ብቻ በውድም ሆነ በግድ እንድንጋተው በተገደድንበት በዚያን ዘመን ሆነ ዛሬ በዕውቅ የወግ ሥራዎቹ የህይወትን ጐምዛዛነትና ጫና ሊያቀልልን የጣረ የጥበብ ሰው ነው፡፡
መስፍን ሀ/ማርያም ሕይወትን፣ ተፈጥሮን፣ ኑሮንና እነዚህን የሚያጫፍሩትን ዐብይት ክስተቶች ከግለሰብ እስከ ህብረተሰብ ባለው ማንነት ዙሪያ በገሀድ የሚታዩ ድርጊቶችን በመዘርዘር፣ አካባቢያችንና ዘመናችንን በይበልጥም በሰዋዊ ማንነታችን ስንቀበለው በምንችለውና በሚያረካ ኪነታዊ ጉዞ እንድንቃኝ ያደረገ የጥበብ ጀግናችን ነው፡፡
መስፍን ሀ/ማርያም በሥነ - ወግ፤ ቋንቋችንን የፈተሸ፣ ተራ ቃላት የምንላቸውንና ልንዘነጋቸው የተቃረቡ ዘየዎችን መልሰው ነፍስ እንዲዘሩ ያደረገ የቋንቋ ጠቢብ ነው፡፡
የመስፍን ሀ/ማርያም ወጎች ሁላችንም የምናቃቸው በቋንቋቸው ማራኪና በአቀራረባቸው ሚዛናዊነት፣ በምርጥ ምሳሌያቸው፣ በምጣኔያቸውና ማዝናናት በመቻላቸው ነው፡፡ በተለይ ሥነ - ወግ ዋነኛው ባህሪይው ማዝናናት መሆኑን የምንረዳው ከመስፍን ሀ/ማርያም ጽሑፎች ነው ብንል አልተሳሳትንም፡፡
ማዝናናት ሲባል ፈገግ ማስደረግን፣ ማሣቅን የሚያጠቃልል ቢሆንም ከዚህ በዘለለ የመስፍን ሃ/ማርያም ወጐች በተራነት የማይጠበቅ ት.ግ.ር.ም.ት፣ የማይረሳ አድናቆትና “እንዲህ ነው ለካ” የሚያሰኝ የመንፈስ ደስታ እያላበሱንና እነዚህንም ዘና ባልንበት እያዋዙ፣ ዘና ባልንበት ቁምነገሮችን አሾልከው እየወረወሩ፣ ነፍስና ስጋችንን እያጫወቱ፣ ለብዙ ዘመን ያሸጋገሩን ናቸው፡፡
ተውኔት የቤተ-መቅደስና የቤተ መንግስት ዜና መዋዕል ዘጋቢ ብቻ ከመሆን ታላቋ ፊቷን ወደ ዝቅተኛው የሕብረተሰብ ሕይወት እንድታዞር ፋና ወጊውን ሥራ የፈፀሙ እንዳሉ ሁሉ፣ መስፍን ሀ/ማርያም በተለይ በተለይ በሥነ - ወግ ስራዎቹ የድሐውን ሕዝብ ጓዳ - ጐድጓዳ በርብሮ፣ የድሀ ወገናችንን ወግና - ታሪኩን ደስታና - ሀዘኑን ሕይወትና - ሞቱን በቅርበት እንድንረዳ ያጋዘን የዘመናችን የወግ አባት ነው።
ከሁሉም ከሁሉም የወግ አባቱ መስፍን ሃ/ማርያም፣ ጥበብን - እምነቱ፣ ጥበብን ትሁት ተሰጥኦው…ጥበብን ለይስሙላ ተሳልሟት ያለፈ፣ ገባ - ወጣ እያለ የጐበኛት ሳይሆን በጥበብ ፍቅር ወድቆ (ላይፈታት ተክሊል ደፍቶ) ላይፈታት ቁርባን፣ ቃል ኪዳን ቋጥሮ - ሳይፈታት፣ እድሜ ህይወቱን የሰዋላት ሰው ነው፡፡
መስፍን ሀ/ማርያም በ1937 ዓ.ም ከአባቱ ከአቶ ሀ/ማርያም ሞገስና ከእናቱ ከወ/ሮ ደስታ አየለ ተወልዶ ባለፈው እሁድ በ69 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡ ጋሽ መስፍን ከ1ኛ እስከ 7ኛ ክፍል ድረስ ሞጆ አንደኛና መለስተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ከ8ኛ ክፍል ጀምሮ የ2ኛ ደረጃ ትምህርቱን እስካጠናቀቀበት ቀን ድረስ በአንቦ እንዲሁም ከ1958 ዓ.ም እስከ 1962 ዓ.ም በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ - ጽሑፍ የመጀመሪያ ዲግሪውን የማዕረግ ተሸላሚ ሆኖ አጠናቋል፡፡
ጋሽ መስፍን በ1964 ዓ.ም ባህር ተሻግሮ ካናዳ ቫንኩቦር በሚገኘው በብሪቲሽ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ልቦለድን፣ ኢ-ልቦለድን፣ ተውኔትንና ሥነ - ግጥምን የጥናቱ ትኩረት በማድረግ “በፈጠራ ሥነ ጽሑፍ” (creative writing) የማስተርስ ዲግሪውን በ1966 ዓ.ም አግኝቷል፡፡
ጋሽ መስፍን ሀ/ማርያም በሥራው ዓለም ለ3 ዓመታት በኤርትራ በተለይ በአስመራና በምፅዋ የአማርኛ ቋንቋን አስተምሯል፡፡
ከ1963-1976 በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋዎች ጥናት ተቋም የተለያዩ የሥነ - ጽሑፍ ኮርሶችን ያስተማረ ሲሆን ከዚህ ጐን ለጐን በኢትዮጵያ ሬዲዮና በኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ሲሰራ ቆይቷል፡፡
ጋሽ መስፍን በድርሰት ዓለም “የቡና ቤት ሥዕሎች”፣ “አውደ ዓመት”፣ “የሌሊት ድምጾች”፣ እና ሌሎች የወግ መጽሐፍትን አበርክቶልናል፡፡ “አዜብና ሌሎች አጫጭር ልቦለዶችን”፣ እንዲሁም የተረት መጻሕፍትን አሳትሟል፡፡ “በቆንጆ ልጅ ፈተና” ሥነ - ግጥሙም እናውቀዋለን፡፡
ጋሽ መስፍን ወደ 550 የሚጠጉ የተለያዩ መጣጥፎችን በጋዜጦችና በመጽሔቶች ላይ በማውጣት ከዘመን ዘመን እያጫወተና እያስተማረ አሸጋግሮናል፡፡ ጋሽ መስፍን ከድርሰቶቹ በተጨማሪ ሃያሲም ነበር፡፡ ጋሽ መስፍን ሳይቤሪያ በዘመተው የኢትዮጵያ የሰላም አስከባሪ ጦር ጋር በመዝመት በአስተርጓሚነት አገልግሏል፡፡
የአብራኩ ክፋይ የሆኑ የሁለት ወንድ ልጆችና የአራት ሴት ልጆች አባትም ነው፡፡
ጋሽ መስፍን በመጨረሻዎቹ የእስትንፋስ ሰዓታቱ ልጁን ሀ/ማርያም መስፍንንና ቃልኪዳን መስፍንን አሳድጉልኝ፣ ለወግ አብቁልኝ እያለ ሲወተውትና ሲማፀን ነው ሕይወቱ ያለፈችው፡፡
ጋሽ መስፍን The Merchant of Fear የምትሰኝ አጭር ልቦለዱንና ሌሎች ያልታተሙ ሥራዎቹ ለንባብ ይበቁለት ዘንድ ሲማፀን ቆይቶ ለአንዴና ለሁሌም ተለይቶናል፡፡
ይህ ሁላችንም የምንወደው፣ ይህ ትሁት፣ ይህ ቅን፣ ይህ የኑሮ ጫና ሳይበግረው ዘመኑን ሙሉ ያገለገለንን ታላቅ የጥበብ ሰው፣ የመጨረሻ ሰዓት ኑዛዜውን ያገለገለው የሀገራችን ህዝብና የጥበብ ወዳጆች ሁሉ እውን እንደሚያደርጉት የፀና እምነቴ ነው፡፡
በመጨረሻም በዚህ በታላቁ የጥበብ ሰውና የወግ አባት በሆነው በደራሲ መስፍን ሃ/ማርያም የቀብር ስነስርዓት ላይ ተገኝታችሁ ቤተሰቦቹን ያጽናናችሁትን ሁሉ በልጆቹ፣ በዘመዶቹ፣ በኢ.ደ.ማ አባላት፣ በራሴና በጥበብ ወዳጆች ሁሉ ስም ላመሰግን እወዳለሁ፡፡
ታላቁ አምላክ ይህን ፍዳውን ሁሉ በምድር ዓለም የጨረሰን የጥበብ አባት መስፍን ሃ/ማርያምን ነፍሱን በገነት ያሳርፋት ዘንድ እንለምናለን፡፡
አመሰግናለሁ

Published in ጥበብ
Saturday, 19 July 2014 12:41

የጋሽ መስፍን ናፍቆት!

እንዲህ ተጫጭሰን
እንዲህ ተጨናብሰን
ውሃ እንዳለዘዘን
ከውሃ ተዋግተን ተዋግተን…ተዋግተን
ውሃን አሸንፈን፤
እሳትን ፀንሰን
እሳትን አምጠን…አምጠን …አምጠን
እሳትንም ወልደን፤
እሳትንም ሁነን፤
ካጮለጮልንለት የድሃውን ጐጆ፣ ቀሣ ከል ጭራሮ
ካበስልንለት ዘንድ፣ የአርሶ አደሩን ንፍሮ
የሰርቶ አደሩን ሕዝብ፣ ለስሰስ ያለ ሽሮ፣
ታሪክ ይዘምረው የኛን እንጉርጉሮ፡፡
ዘመን ይመስክረው፣ የኛን ውጣውረድ
    የእንግልት ኑሮ፡፡
ደበበ ሰይፉ “የክረምት ማገዶች”
ደራሲና ሃያሲ መስፍን ሀብተማርያም በሀገራችን ሥነ - ጽሑፍ ደማቅ ታሪክ ያለው፣ በተለይም በወግ ጽሁፎቹ የሚታወቅና በርካታ መጽሐፍትን ለሕዝብ ያቀረበ ሰው ነው፡፡ ልቡ ወደ ደሳሳ ጐጆዎች፣ ሃሳቡ ወደምስኪኖች ድንኳን ገብቶ፣ የየዕለት እንጀራውንና ኑሮውን፣ አንብቦ ጽፎልናል፡፡ ዓውደ ዓመትና አዘቦቱን፣ ክብሩንና ውርደቱን አሳይቶናል፡፡ የሚያሳዝነውን ሕይወት፣ የትራጀዲውን ሥዕል ቀለም ነክሮ እያሳቀና እያስደመመ ጠቢብነቱን አስመስክሯል፡፡ ጋሽ መስፍን የዩኒቨርሲቲም መምህር ነበር፡፡ ለዚያውም ጐበዝ መምህር! ብቻ አንዳንዴ ክፍል መግባቱ አይሆንለትም ነበር! ግና ተማሪዎቹ ሲናገሩ” አንዴ የገባ ቀን ግን አፍርጦ ያስተምራል፡፡ ጨምቆ ያቀብላል” ይላሉ፡፡ ይህንን ነገር ጋሽ መስፍንም ያውቃል፡፡ “ለምን ነበር የምትቀረው?” ስትሉት ይነግራችኋል፡፡ ግንባሩን ሸብሸብ አድርጐ፣ አይኑን በትኩረት በናንተ ላይ ተክሎ፡፡ ምክንያቶቹ ሁሉ አሳማኝ ነበሩ፡፡ ብዙዎቹ የሕይወቱ መንገዶችም አሳዛኝ ናቸው፡፡
በተለይ ያለፉትን ዘመናት መጽሔቶች፣ በተለይ “የካቲት”ን ስታገላብጡ፣ የሠራቸውን ሂሶች አድናቆት ይፈጥሩባችኋል፡፡ ጋሽ መስፍን ደፋር ነው፤ በተለይ በትርጉም ሥራዎች ላይ የሠራቸው ሂሶች ግሩም ነበሩ፡፡ ስለ ፈሊጣዊ አነጋገር ብቁ ዕውቀት የሌላቸው ሰዎች ተርጉመው ያስነበቡንን ገላልጦ ሲያሳይ አጀብ ያሰኛል፡፡
በተለይ ደግሞ ሲያወራ እንዴት እንደሚመስጥ የቀረባችሁት ሰዎች ታውቁታላችሁ፡፡ ስለ ድሮ አራዶች፣ ስለ ሰካራሞች፣ ስለ ጥላሁን ገሰሰ፣ ስለ ወጣትነት ፍቅር… ብዙ ብዙ ነገር ያወራል፡፡
ከሁሉ የሚገርመው ግን ያ አይደለም፣ ያ በተቀላጠፈ ንግግር በአራዳ አይኖችና ከናፍርት የሚያስደንቃችሁ ጋሽ መስፍን ድንገት የሚያሳዝን ነገር ሲገጥመው፣ ያ ወደ ውስጥ የራቀው አንጀቱ ይንሰፈሰፋል፡፡ “አፈር ልብላ!” ይላል፡፡ የጋሽ መስፍን ርህራሄና ደግነት ልክ የለውም፡፡ ልዩ ሰው ነው፡፡
ብዙ ጊዜ ሰዎች በአፀደ ሥጋ ሲለዩን ደግ ያልሆኑትን ደግ፣ ቸር ያልሆኑትን ቸር ማለት የተለመደ ነው፡፡ እኔ ግን ይህንን ልማድና ስርዓት አልቀበለውም፡፡ ክፋትን ደግነት ነው ብሎ መናገር በራሱ ለሕሊና ወንጀል ነው፡፡ ለነፍስ መራራ ነው። ይሁንና ክፉ የምንለው ሰው እንኳ ጥቂት ደግ ነገር አያጣውም፡፡ ምናልባትም ባይሞት በአንድ ነገር ሊጠቅመን ይችላል ብለን በቅንነት ልናስብ እንችላለን፡፡ ጋሽ መስፍን ግን - ከልቡ ቅንና የሚራራም ሰው ነበር፡፡  
ከረጅም ዓመታት በፊት ዩኒቨርሲቲ ሲያስተምር ሳለ አንድ ቮልስ ዋገን መኪና ነበረችው። እና ያቺን መኪና ከግቢ ውጭ ራቅ አድርጐ ያቆማል፤ እንደዚያ የሚያደርገው ደግሞ መኪናዋ የኋላ ማርሽዋ ስለማይሰራ ነው፡፡ ሕዝቡ ግን “መስፍን ነው ሰው ማለት፤ መኪናዬን እዩልኝ ብሎ ፊት ለፊት አይገትርም፣” ብለው ያደንቁታል፡፡ ጋሽ መስፍን ይህንን ያወራልኝ አውቶቡስ ተራ አካባቢ በነበረውና ሁልጊዜ ተቀምጦ (በተለይ ከሰዓት) በሚያሳልፍበት የጓደኛው ሆቴል ውስጥ እየሣቀ ነበር፡፡
ጋሽ መስፍን “የአፍሪካ ፀሐይ” መጽሔት ዋና አዘጋጅ ሆኖ በሚሠራበት ጊዜ፣ እኔ መጣጥፍ አቅራቢ ሆኜ ጽጌረዳ ሃይሉና ሶስና አሸናፊ (ጋዜጠኞች) በኋላ ደግሞ ጋዜጠኛ ገዛኸኝ መኮንን በየዕለቱ እንገናኝ ነበር፡፡ ምናልባትም ያኔ ባይሰንፍ ኖሮ የሕይወት ታሪኩን ለሕዝብ የምናቀርብበት ጊዜ ከዛሬ በቀደመ ነበር፡፡ ግን “ቆይ’ስቲ” ይላል። እዚያ ሠፈር ቤተኛ እስክሆን፣ ወዳጆቹን ሁሉ እስክግባባ ድረስ ተዛምደን ነበር፡፡ በኋላ ግን እኔ ድሬደዋና ናዝሬት ለሥራ የሄድኩባቸው ዓመታት ለመራራቃችን በር ከፈቱ፡፡ አሁን ሳስበው “እንኳን ተራራቅን” እላለሁ፡፡ በያኔው መንፈስና ቅርበት ብሆን ኖሮ ሀዘኑን እንዴት እችለው ነበር?
ጋሽ መስፍን ነገሮቹ ያሳዝናሉ፣ ያስቃሉ፡፡ እንደብዙዎቹ የሥነ ጽሑፍ ሰዎች ነፍሱ ቅብጥብጥ ናት፡፡ ጥርሳቸውን ነክሰው ለንግድ የሚጽፉትን ነጋዴዎች ማለቴ አይደለም፤ ውስጣቸው እየነደደ የሚያበሩትን እሣቶች እንጂ!
ከጥቂት አመታት በፊት በፓትርያሪኩ ቢሮ ለሥራ ተቀጥሮ በነበረ ጊዜ የተሰማው መንታ ስሜት ሳስበው ይደንቀኛል፡፡ በአንድ በኩል ጥሩ ክፍያ፣ ለቀጣዩ ዘመንም ጥሩ ዕድል ከፊቱ ሲደቀን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የቤተክርስቲያኒቱ ሥርዓት የሚፈልገው ሥነ ምግባራዊ ጥንቃቄ አስጨንቆት ነበር፡፡ እዚያ ቢሮ ከገባ በኋላ ከአራት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ፊት ለፊት ካለው ዩኒቨርሳል መጽሐፍ መደብር ጐን ካለው በርገር ቤት በር ላይ ተገናኘን፡፡ እንደሌላው ቀን ዘና ብዬ ሠላም ልለው ስል - እጄን ይዞ እንዳሞራ አስገባኝ፡፡ በሲጋራ ጥም ተንገብግቧል፡፡
“ተሰቃየሁ!” አለኝ ግንባሩን ሸብሽቦ፡፡ “ከነጋ ገና ሁለተኛ ላጤስ ነው፡፡ መውጫ የለም፤ ይገርምሃል… ሰውየው ግን ውጭ ሀገር ሁሉ ለሥራ ሊልኩኝ ያስባሉ፤ ከተወሰኑ ወራት በኋላም ለራሴ መኪና ይሰጠኛል፡፡ ግን ከበደኝ፡፡” ብሎ በራሱ ተማረረ፤ አዘነ፡፡ ጋሽ መስፍን ገርነቱ ያሳዝናል፤ እውነተኝነቱ ይገርማል፡፡ ቀርበው ያዩት ሁሉ ጋሽ መስፍንን ከቸልተኝነቱ በስተቀር በምንም ሊከስሱት አይችሉም፡፡ ጋሽ መስፍን ሰው ያከብራል፣ ሰው እንዲያከብረውም ይፈልጋል፡፡ የሰው መብት አይነካም፤ እንዲነኩበትም አይፈቅድም፡፡ ገንዘብ እንዲኖረው ይፈልጋል፣ ባይኖረውም ግን ነፃነቱን አይሸጥም ሲበሣጭ ቀበቶውን በሁለት እጆቹ ከፍ ከፍ እያደረገ ይንቆራጠጣል፡፡ ጋሽ መስፍን ደግ ነው፤ ለሰዎች መልካም ማድረግ ይወዳል፡፡ “ብልጥ ጀንበር” የሚለውን መጽሐፌን ሳሳትም የፍቅር ደብዳቤዎችን ማካተት በሀሳቤም አልነበረም፡፡ ጋሽ መስፍን ነው “አንጀት ይበላሉ” ብሎ አብረህ አሣትመው ያለኝና የጀርባ አስተያየት የፃፈልኝ፡፡ ያ ብቻ አይደለም፤ ቸልተኛ ነው ብዬ የምጠረጥረው ጋሽ መስፍን አዲስ አድማስ ላይ የምጽፋቸውን መጣጥፎች እያነበበ፤ በግንባርና በስልክ አስተያየት ሰጥቶኛል፡፡ ከዚያም ባለፈ ስለ እኔ ጥሩ ምስክርነት በመስጠት በትርፍ ጊዜዬ በአንድ ጋዜጣ ላይ በአርትኦት ሥራ እንድቀጠር በማድረግ ተጨማሪ ገቢና ሥራ እንዳገኝ አግዞኛል፡፡
ከዚህም ባለፈ የሕይወት ታሪኩን ብዙ አጫውቶኛል፡፡ ግና ሰው ተፈጥሮ ማለፉ አይቀሬ ነውና ጋሽ መስፍን ታምሞ ሳልጠይቀው በማለፉ ከልብ አዝኛለሁ፡፡ የጋሽ መስፍንን ሕልፈት የነገረኝ ገጣሚው ወዳጄ ታገል ሰይፉ ነው፡፡ ታገል ከጋሽ መስፍን ሞት ቀደም ባለው ሣምንት መታመሙን ሲነግረኝ፤ በዚህ ሣምንት ሄደን እንድንጠይቀው አደራ ብዬው ነበር፡፡ ግን ክፍለሀገር ደርሼ ስመለስ ጋሽ መስፍን በሞት መለየቱን አረዳኝ፡፡
ከታገል ሰይፉ የምወድለትን አንድ ባህሪ ያስታወስኩት ይሄኔ ነው፡፡ ታገል ሰው ሲሞት እምብዛም አያለቅስም፡፡ ሰው ሲታመም ግን ደጋግሞ ይጠይቃል፡፡ የሚችለውን ነገር ሁሉ ያደርግለታል። ከዚያ በኋላ “በቃ ሆነ” ይላል፡፡ እውነቱን ነው፡፡ ሰውን መጠየቅ በሕይወት ሳለ ነው፡፡
ያ - ቀልድ አዋቂ፣ ያ- ገራገር ጋሽ መስፍን፤ በቀላሉ እንደሚለየን አልገመትንም ነበር፡፡ ለአስተርጓሚነት ከላይቤሪያ ሄዶ ሲመለስ ጦር ሃይሎች ሆስፒታል ታሞ ሊጠይቁት ከሄዱት ሰዎች ውስጥ ጋዜጠኛና ደራሲ ሶስና አሸናፊ አንዷ ነበረች፡፡ ጋሽ መስፍን እንዲህ ብሏት ነበር፤ “አትሥጉ ከሰባ ዓመት በላይ ሳልዘጋ አልሞትም!...ቤተሰባችን ሁሉ ሰባ ይገባል!” ግን እንዳለው አልሆነም! በ69 ዓመቱ  - ሕይወቱ ተደመደመ! ያሳዘነኝ ነገር ቢኖር የጋሽ መስፍን ናፍቆት ነው፡፡ ባገኘሁት ቁጥር አንድ የሚለኝ ነገር ነበር። “አንድ ኖቭል ሳልጽፍ አልሞትም!” ግን ናፍቆቱን አላገኘም፤ ተስፋውን አልጨበጠም! ዋ ጋሽ መስፍን!  


Published in ጥበብ
Saturday, 19 July 2014 12:35

የተማሪው ምኞት

የአምስተኛ ክፍል የአማርኛ አስተማሪ የሆነው ዳዊት፣ ለተማሪዎች ስለደብዳቤ አፃፃፍ ካስተማራቸው በኋላ ለሚወዱት ሰው ደብዳቤ እንዲፅፉ አዘዛቸው፡፡ ከ10 ማርክ የሚያዝ ነው፡፡
ተማሪዎቹ፣ ደብዳቤ መጻፍ ጀመሩ፡፡
ዳዊት፣ ተማሪዎቹ ከፃፏቸው ደብዳቤዎች መካከል፣ የአንዱ ተማሪ ደብዳቤ  በጣም አስገረመው። በአንዲት ብጣቂ ወረቀት ላይ ያሰፈረውን ሃሳብ ከአንድ የአምስተኛ ክፍል ተማሪ የመጣ ነው ለማለት ከብዶት፣ ደብዳቤውን ቤቱ ሆኖ ከአስር ጊዜ በላይ ቢያነበውም፣ አሁንም ከትምህርት ቤቱ ካፍቴሪያ ተቀምጦ ለሁለተኛ ጊዜ ደግሞ እያነበበው ነው፡፡
‹‹መምህር እኔ ለራሴ ብዙ የምመኛቸው ነገሮች ቢኖሩኝም ከሁሉም በላይ ግን እንዲሳካ የምመኘው ነገር ቢኖር ለኔ ሳይሆን ለእትዬ ነው፡፡ እትዬ ማለት እናቴ ነች፡፡ ስሟ እቴነሽ ሲሆን አባቴ በህይወት እያለ እቴ ብሎ አቆላምጦ ነበር የሚጠራት፡፡ እኛም ከሱ አፍ ለምደን ይሁን ልጅ እያለን እንድንጠራት አስተምራን ይሁን፣ ሳናውቀው እቴ እያልን ነው የምንጠራት፡፡ እቴ ብሎ የማይጠራት ሰው ለሷ ጥሩ አመለካከት እንደሌለው አድርጋ ነው የምትወስደው።
‹‹እኔ ለእቴ የምመኝላት ነገር ብዙ ቢሆንም በጣም አጥብቄ የምመኝላት ነገር ግን ሁሌ ስትስቅ እንዳያት ነው፡፡ ሁሌ እንድትስቅ ሊያደርጋት የሚችለውን ነገር ደጋግሜ ሳስብ የመጣልኝ ደግሞ ባል ነው፡፡ እናቴ ልክ እንደ አባቴ የምትወደው ባል ብታገኝ በጣም ደስተኛ የምትሆን ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም እናቴ እኛን ለማሳደግ ብቻዋን ስትለፋ ከሚፈጠርባት ጭንቀት የተነሳ ብዙ ጊዜ ስትስቅ አይቻት አላውቅም፡፡ አንዳንዴ እንኳን የምትስቀው ስላለፈው ጊዜ ስታወራና ስለ አባቴ ስትናገር ነው። ከዚያም አልፎ ከአባቴ ጋር ተቃቅፋ የተነሳቻቸው ፎቶዎች ላይ ያለው ምስሏ ብቻ ነው፡፡ እሱን ሳይ እትዬ እንደሳቀች አስባለሁ፡፡
‹‹ጥርሶችዋ እኮ ሲያምሩ፡፡ እኛ ክፍል ካሉ ሴቶች ሁሉ በጣም የሚያምር ጥርስ አላት የምትባለዋ ሳምሪ እንኳን ጫፍዋ ጋ አትደርስም፡፡ ይህን የምለው ያለማጋነን ነው፡፡
“መምህር ዳዊት፣ ማኪያቶህ እኮ ቀዘቀዘብህ” አለች ከፊቱ ተገተረች፤ የአስተማሪዎች ካፌ ባለቤት የሆነችው አልማዝ፡፡
ዳዊት በእጁ ከያዘው ብጣቂ ወረቀት ተላቆ፣ ቀና ብሎ ተመለከታት፡፡ ደብዳቤው ላይ የተገለፀችው እናትና ከፊት ለፊቱ የቆመችው አልማዝ፣ በዕድሜ እንደሚቀራረቡ ገመተ፡፡ በባህሪ ግን የተማሪው እናት ከዚች ትልቃለች፤ እ… ሷ… እ… ኮ…
“ዛሬ ምን ሆነሀል? እኔ ላይ መንቀባረርህ እንኳን የተለመደ ነው፡፡ የሰራሁልህ ማኪያቶ ላይ እንደዚህ መኩራትህ ግን በጤና አይመስለኝም፡፡” ብላ ፈገግ ስትል፣ በሽቦ የታጠረ ገጣጣውን ጥርሷን አይቶ ፈጠን ብሎ ዐይኑን ወደ ማኪያቶው አሸሸው፡፡ ማኪያቶውን አንስቶ ሲቀምሰው ቀዝቅዟል፡፡
“ሳይቀዘቅዝ አይቀርም፡፡ ላሙቅልህ?”
“ደስ ይለኛል” ፈጠን ብላ አነሳችው፡፡
“ግን ሰላም ነው? ዛሬ ፈዘሃል” ደግማ ጠየቀችው።
“ሰላም ነው” አላት ቶሎ እንድትሄድ ስለፈለገ ፊቱን ፈገግታ ነስቶ፡፡ ፊት ቢነሳትም አልገባ ያላት አልማዝ እያጉረመረመች ሄደች፡፡ ዳሌዋን እያማታች ወደ ማሽኑ ስትራመድ ያለችውን ባይሰማትም ጀርባዋ ላይ የተተከሉት ዐይኖቹ ግን ይህ ዳሌ ባይወዛወዝ ማጐምጀቱ ከፍ እንደሚል እያሰበ፣ ለሁለት ቀን በሃሳቡ ስትመላለስ የነበረችው እትዬ፣ ሥርዓት ባለው አኳኋን ስትራመድ በሃሳቡ ተመለከታት፡፡
“ምን እየሆንኩ ነው? ስንት ቆንጆ ሴቶችን ፊት እየነሳሁ ያበረርኩት ኮስታራው ሰውዬ፣ በልጅ ጽሑፍ የተገለፀችውን አንዲት እናት ላፈቅር? ኧረ አይሆንም” አለ ለራሱ ብቻ በሚሰማ ድምፅ፡፡
“ኖ… ኖ ስለ ‘ሷ ካሁን በኋላ ማሰብ የለብኝም” ብሎ ወደ ብጣቂዋ ወረቀት ዐይኖቹን ላከ፡፡
“እትዬ የጠይም ቆንጆ መሆንዋን ብዙ ሰዎች ሲያወሩ ሰምቻለሁ፡፡ እንዲያውም ባለ ሱቁ አብደላ፣ የኢትዮጵያ ቁንጅና ውድድር አሸናፊ ከሆነችዋ ሃያት አህመድ ጋር ብትወዳደር እንደምትበልጣት አልጠራጠርም ብሎኝ ነበር፡፡ እኔ የሚያሾፍ መስሎኝ ስስቅ፣ “ዕውነቴን እኮ ነው ወላሂ! በጣም ነው የምትበልጣት” ብሎ ተቆጣኝ፡፡ እኔም አመንኩት ምክንያቱም ሙስሊሞች ወላሂ ብለው እንደማይዋሹ አውቃለሁ፡፡”
ዳዊት ወረቀቱን ለሁለት አጥፎ ጠረጴዛው ላይ አስቀመጠው፡፡
“ይህ ልጅ እያላገጠብኝ ይሆን እንዴ? ለነገሩ እንዴት ሊሆን ይችላል፡፡ የእኔን የሴት ምርጫ ማን ሊነግረው ይችላል? ምርጫዬን ለቅርብ ጓደኞቼ ብቻ ነው የተነፈስኩት፡፡ በደብዳቤው ላይ ያለችው ሴት፣ የሴት ውበት ምርጫዬን ሁሉ እኮ ነው የምታሟላው። ነገ ወላጅ እንዲያመጣ አስገድጄው ካልተዋወቅኋት  የሆነ ቅዥት ውስጥ ገብቼ ማበዴ የማይቀር ነው” ብሎ ሰዓቱን ተመለከተ “ያ የተረገመ ፈልፈላ ወዳለበት ክፍል ለመግባት አርባ አምስት ደቂቃ ይቀረኛል፡፡” ብሎ ተማረረ፡፡
የሆነ ፍርሃት በውስጡ ሲላወስ ተሰማው፡፡ እያሰበ ያለውን ነገር ቢያደርገው ከሥነ ምግባር ውጪ እንደሆነ በማወቁ ነው፡፡ በየግምገማው የአስተማሪ ጓደኞቹን ጉድ በይፋ እየተናገረ ሲያሳፍራቸው እና ሲያሳጣቸው የነበረው መምህር፣ራሱ ከሥነ ምግባር ውጪ ሆኖ ቢገኝ ምን እንደሚባል ሲያስበው ጨነቀው፡፡ ይህ እና ይህን የመሳሰሉ የሥነ ምግባር ጉዳዮችን እያሰበ፣ የተማሪውን እናት አስጠርቶ ለመተዋወቅ ያለውን ጉጉት ከባድ አደጋ ቢኖረውም ከማድረግ እንደማይመለስ ወሰነ፡፡ ህሊናውም ዝም ብሎ እጅ ላለመስጠት መግደርደሩ እንጂ፣ የወንድነት ስሜቱ  እንደሚያሸንፍ እርግጠኛ ነበር፡፡
  “ይኸው ማኪያቶህ! ትኩስና ያጐደልከውን በራሴ ወጪ ሞልቼ ነው ያመጣሁልህ››  ብላ ጠረጴዛው ላይ በታላቅ ትህትና አስቀመጠችለት፡፡
“አመሰግናለሁ” ብሎ የማኪያቶውን ብርጭቆ አነሳው፡፡ ማኪያቶውን እንደቀመሰ በጥንቃቄ እየተመለከተችው እንደሆነ ስለሚያውቅ፣ እርሷን ለማስደሰት ሲል ጣዕሙን ሳያጣጥም፣ “በጣም ይጣፍጣል” ብሎ ጠቀሳት፡፡ በፈገግታ ተውጣ እየተሽኮረመመች ጥላው ሄደች፡፡
የካፌው ደንበኞች የሆኑት አስተማሪ ጓደኞቹ፣ አልማዝ ለእርሱ ያላትን ፍላጐት ተገንዝበው ሲጫወቱባት፣ “ጥርስሽ ቢያምር እኮ ይጠብስሽ ነበር” አልዋት፡፡ እርሷም ሳትውል ሳታድር እንደፀበል ዕቃ ውጪ ያድሩ የነበሩትን ጥርሶቿን ለማሳመር ስትል፣ በአስተማሪ ደሞዝ ሲተመን ከአንድ ዓመት ደሞዝ በላይ በሚሆን ብር ጥርሷን በብረት አሳጥራ መጣች፡፡
“አሁንስ?” አለቻቸው፣ ማኪያቶ በነፃ እየጋበዘች።
“አሁንማ ተስፋ አለሽ” አሏት፡፡ ድጋሚ መጋበዝ ፈልገው እንጂ ጃንደረባው የሚል ቅፅል ስም ያወጡለት ጓደኛቸው ምኞቷን እንደማያሳካላት ያውቃሉ፡፡
ጠቆር ያለ ማኪያቶ በፍቅር የሚወደው ዳዊት፣ በቀድሞ ልማዱ ከጠረጴዛው ላይ ያነሳትን የማኪያቶ ብርጭቆ ወደ ቦታዋ የሚመልሳት በቅጽበት ጭልጥ እንዳደረጋት ነበር፡፡ ዛሬ አንዴ ቀምሶ አስቀመጣት። ብጫቂ ወረቀቷን እያመነታ አነሳት፡፡ ደጋግሞ በማንበቡ ብዛት በቃሉ የሸመደደው ቢሆንም፣ የማንበብ ፍላጐቱን መግታት አልቻለምና ማንበብ ጀመረ፡፡ የወረቀቷ ጀርባ በጣቶቹ ላብ ነጭነቷን ለቃ ቆሽሻለች፡፡
‹‹አንድ የምፈራው ነገር አለ፤ ምኞቴ እንዳይሳካ የሚያደርግ፡፡ የመጀመሪያው ራሷ እትዬ ስትሆን፣ እኛን አሳድጋ ለወግ ለማዕረግ ካልበቃች ሌላ ባል እንደማታገባ ደጋግማ ነግራኛለች፡፡ እትዬ ደግሞ ቃልዋን የማጠፍ ልማድ የላትም፡፡ ሁለተኛ እኛ ነን፤ እትዬን ወዶ የመጣ ወንድ እኔን እና ሁለት ወንድሞቼን ጠልቶ የሚሸሽ ይመስለኛል፡፡ ሦስተኛው ችግር ግን ትንሽ ቀለል ያለ ቢሆንም፣ ከችግሮቹ መካከል እንደ አንዱ መታየት ይችላል፡፡ እትዬ በገባችው ቃል ላይ አንድ ተአምር ተፈጥሮ የሆነ ሰው ወዳ ብታመጣ እኛ ጠልተነው ችግር እንዳንፈጥርባት እፈራለሁ፡፡
‹‹አምላኬ አሁን የጠቀስኳቸውን ችግሮች አልፎ የግልዋ ባል ይስጣት እንጂ፣ በእኛ በኩል የሚገጥማትን ችግር እኔ እንዲስተካከል አደርጋለሁ፡፡ በፍፁም በየትኛውም መንገድ እኛ ለእርሷ እንቅፋት እንደማንሆንባት ደጋግሜ ቃል እገባለሁ፡፡
‹‹አምላኬ እባክህን ለእትዬ የእኔ የምትለውን ሰው ስጣት! በአሥራ ሰባት ዓመቷ ተድራ በማከታተል ሦስት ልጆችን ወልዳለች፡፡ ስምንት ዓመት የቆየው ትዳርዋ በሚያሳዝን መንገድ ከተቋጨ አምስት ዓመት ሞላው፡፡ ታዲያ አታሳዝንም? ገና እኮ አንድ ፍሬ ልጅ ነች፡፡ ብዙ ደስታ ማግኘት አለባት፡፡ እባክህ አምላኬ አንድ መልዓክ መሳይ ተወዳጅ ሰው ላክላት፡፡››
 ዳዊት ካቀረቀረበት ወረቀት ቀና ሳይል የተጀመረው የትምህርት ክፍለ ጊዜ መቋጨቱንና የሚቀጥለው የሚጀምርበት ሰዓት መድረሱን የሚያስተጋባው ኤሌከትሮኒክ ጡሩንባ አንባረቀ፡፡ በሰማው ድምፅ ተደስቶ፣ የጀመረውን ማኪያቶ ጠጥቶ ሳይጨርስ፣ ከካፌው በፍጥነት ወጣ፡፡
       አምስተኛ ‹‹ሀ›› የሚል ፅሑፍ በሩ አናት ላይ የተለጠፈበትን ክፍል ከርቀት ሲመለከት ደነገጠ፡፡ ሩጫ የሚመስል ፈጣን እርምጃው ወደ ሕፃን ልጅ ዳዴ በአንድ ጊዜ ተቀየረ፡፡ ሁልጊዜ ለመግባት የሚጓጓለት ክፍል መሆኑን ዘነጋው፡፡ የልቡ ምት እንደ ትግርኛ ዘፈን የሙዚቃ ምት ‹‹ድም፣ ድምድም… ›› እያለ ነው፡፡
‹ብመለስስ… ኖ… ኖ… ኖ… ለምን አይቀርብኝም? በቃ ገብቼ እንደ ዱሮዬ አስተምሬ እወጣለሁ፡፡ ኖ…ኖ… ኖ ይሄማ ቀሽምነት ነው› ብሎ መራመድ እንደጀመረ ድንገት ፈገግ አለ፡፡
“ወንዳታ! አሪፍ ሃሳብ… እንዲያውም እንዲህ ነው የማደርገው…” ብሎ በፍጥነት እየተራመደ ወደ ክፍሉ ገባ፡፡ እርሱ ሲገባ በክፍሉ ይሰማ የነበረው ጫጫታ ከመቅፅበት “ፖዝ›› አደረገ፡፡ ከሰኮንዶች በፊት የጠፋው ፍርሃቱ፣ የፈረስ ኮቴ በሚመስል ምት፣ ልቡን እየደለቀ መጣበት፡፡ ተማሪዎቹን ቀና ብሎ ማየት ፈርቶ እንዳቀረቀረ የክፍሉን አለቃ ጠርቶ እንዲከተለው ነግሮት ወጣ፡፡ የክፍል አለቃው ወጥቶ በጭንቀት የሚንጐራደደውን መምህሩን በአትኩሮት ተመለከተው፡፡ መምህሩ እጁ ላይ ያለውን የተማሪዎች ደብዳቤ ዘረጋለት፤ አለቃውም ተቀበለው፡፡
“እ… ይኸውልህ የቤት ሥራው ታርሟል፡፡ ስማቸውን እየጠራህ ለሁሉም ስጣቸውና ስትጨርስ እያንዳንዳቸው በተራ ቁጥራቸው እየተነሱ የፃፉትን ደብዳቤ እንዲያነቡ አድርግ! እኔ ትንሽ ስላመመኝ ዛሬ አላስተምርም” ብሎ ሳይጨርስ አለቃው ወደ ክፍሉ ሊገባ ሲል በፍጥነት ጠራው፡፡
“አቤት ቲቸር”
“እ… እ… ዮሐንስ ደስታን ጥራልኝ”
አለቃው ራሱን በአዎንታ ነቅንቆ ወደ ክፍሉ ገባ፡፡ መርዶ ለመናገር የተላከ መልዕክተኛ ይመስል እየተቁነጠነጠ፣ ሰረቅ እያደረገ ወደ በሩ ሲመለከት፣ ከተጠራው ተማሪ ጋር ዐይን ለዐይን ተጋጩ፡፡ መምህር ዳዊት ሲሰርቅ እንደተያዘ ሌባ በፍርሃት ዐይኖቹ ማረፊያ አጥተው ተረበሹ…
“አቤት ቲቸር” ዮሐንስ ተናገረ፡፡
“እ… እ… ነገ ጥዋት ወላጅ እንድታመጣ”
ተማሪ ዮሐንስ፣ መልሱን ሳይሰማ በእፎይታ መክነፍ ሲጀምር፣ መምህሩ አንድ ነገር ትዝ ብሎት ባለበት ተገተረ፤ “ወላጅ እኮ ነው ያልኩት! ሌላ ሰው ይዞ ቢመጣስ? ምን አይነት መከራ ውስጥ ነው የገባሁት? …   ድጋሚ ላስጠራው? እያለ በሃሳብ ሲደናበር፣
“ቲቸር ምን አጥፍቼ ነው?” የሚል አሳዛኝ ድምፅ ሰማ፡፡ ዳዊት ሲዞር  ሹራብ የለበሰ ጠይም ልዑል የመሰለ ሕፃን፣ ዕንባ ያቀረሩ ትላልቅ ዐይኖቹን መደበቅ ተስኖት ይከተለዋል፡፡ ዮሐንስን ሲመለከት ከሀዘኔታ ይልቅ በውስጡ የታሰበው እናቱ እንዴት በሥርዓት እንዳሳደገችው ነበር፡፡
“ይኸውልህ ዮሐንስ እናትህን አምጣ ያልኩህ ስላጠፋህ ሳይሆን ጉብዝናህን ለእናትህ ነግሬ ላሸልምህ ፈልጌ ነው፡፡” ዮሐንስ በሰማው ዜና ተደስቶ መዝለል ሊባል በሚችል የሰውነት እንቅስቃሴ ሲፍለቀለቅ፣ ዳዊት ትክ ብሎ ጥርሱን እየተመለከተ የእናቱ ጥርስ ምን እንደሚመስል መገመት ጀመረ፡፡
“ቲቸር! ስለ ደብዳቤው ግን አትነግራትም አይደል!?” ካለ በኋላ በፍጥነት የመምህሩን ጣቶች በአትኩሮት ተመለከተ፡፡
“ብነግራት---ምን ችግር አለው? መልካም ምኞት እኮ ነው የተመኘህላት” ብሎት ፈገግ አለ፡፡ የዮሐንስ አይኖች ካረፈበት ተከትሎት ሲሄድ ግን፣ ከገዛ ራሱ ጣት ላይ አረፈ፡፡ ዮሐንስ ከግራ እጁ ጣት ላይ ቀለበት ሲፈልግ፣ የነበረ ስለመሰለው ተደስቶ ቀና ሲል፣ ዮሐንስ በፈገግታ እንደበራ ዘሎ ተጠመጠመበት፡፡
ዳዊት የሁለት ቀን ፍቅረኛውን ያገኛት ይመስል በሀሴት ተሞላ፡፡ አባት ልጁን እንደሚዳብስ፣ ዳዊትም የዮሐንስን ፀጉር፣ ፍቅር በተሞላባቸው ጣቶቹ በስስት ተመላለሰባቸው፡፡

Published in ልብ-ወለድ

“የኔ ፍቅር” እና “ባህርዳር” የሚሉ ዘፈኖች ይካተቱበታል

አሜሪካዊው የሬጌ ሙዚቃ አቀንቃኙ ቶኒ ዊልያምስ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው የዛሬ 9 ዓመት ገደማ ነበር፡፡ የቦብ ማርሌይ 60ኛ ዓመት ልደት በአዲስ አበባ በተከበረበት ወቅት። በወቅቱ የቦብ ማርሌይ ቤተሰብና ሌሎች ታላላቅ ሙዚቀኞች በተሳተፉበት ትልቅ ኮንሰርት ላይ ሙዚቃውን የማቅረብ ዕድል ባያገኝም ከሪታ ማርሌይ ጋር በናዝሬት ኮንሰርት አቅርቦ ነበር፡፡
ከአንድ ወር ቆይታ በኋላ ወደ አገሩ የተመለሰው ዊልያምስ፤ ዳግም ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ከስድስት ዓመታት በኋላ ነው - በ2012 ዓ.ም፡፡ ለስምንት ወራት ያህል በባህርዳር ከተማ መቀመጡን ይናገራል፡፡ ተወልዶ ባደገባት ካሊፎርንያ እንዲሁም በጃማይካና ሌሎች የካሬቢያን አገራት በሬጌ ሙዚቃ አቀንቃኝነት ከ15 አመታት በላይ ሰርቷል - ቶኒ ዊልያምስ፡፡
ሁለት የሬጌ ሙዚቃ አልበሞችን ለአድማጭ ያደረሰ ሲሆን አሁን ደግሞ “ባክ ቱ ኤደን” የተሰኘውን ሦስተኛ አልበሙን በኢትዮጵያ በመስራት ላይ ይገኛል።
በበጐ አስተሳሰብ የተቃኙ የሬጌ ሙዚቃዎችን የሚጫወተው አርቲስቱ፤ በአውሮፓ፣ በአሜሪካና፣ በካሪቢያን አገራት ተዘዋውሮ፣ ከታዋቂ የሬጌ ሙዚቀኞች ጋር በመስራት ሰፊ ልምድ አካብቷል። ዊልያምስ፤ በአዲስ አበባ “ስኩል ኦፍ ቱሞሮው” የእንግሊዝኛ ቋንቋ ያስተማረ ሲሆን አንዳንዴ በምሽት ክለቦች የሙዚቃ ሥራዎቹን እንደሚያቀርብም ይናገራል፡፡
የሙዚቃ አጀማመሩ
በካሊፎርኒያ ሴሪቶስ ከተማ ተወልዶ ያደገው ቶኒ ዊልያምስ፤ ገና በ13 ዓመቱ ጀምሮ ይጽፋቸው በነበሩ የአብዮተኝነት ስሜትን የሚያንፀባርቁ ግጥሞቹ መነሻነት ወደ ሙዚቃ መሳቡን ያስታውሳል፡፡ ግጥሞቹ መጥፎ ድርጊቶችን የሚያወግዙ፣ ቅንነትንና ሰላምን የሚሰብኩ እንደነበሩም ይናገራል፡፡
በወጣትነት ዕድሜው “ሃርድ ኮር” የሚባሉት የሮክ ሙዚቃዎች ምርጫዎቹ እንደነበሩ ያስታውሳል። የ“ሃርድ ኮር” ሙዚቀኞች እንደ ሬጌ ሙዚቀኞች ስለነባራዊው ሁኔታ የሚያወሱ ግጥሞችን እንደሚጫወቱ የሚያስረዳው ቶኒ፤ ሙዚቀኞቹ ከአብዮተኛነት ስሜቱ ጋር ስለተጣጣሙለት ይወዳቸው እንደነበር ይገልፃል፡፡ ከ1988 እ.ኤ.አ በኋላ ግን የ “ሃርድ ኮር” ሙዚቃዎችን ትቶ ሙሉ ለሙሉ የቦብ ማርሌይ የሬጌ ዘፈኖችን ማድመጥ ጀመረ፡፡ የሬጌ ሙዚቃ ግጥሞች በአብዛኛው ሰናይ ተግባራትንና ቅን አስተሳሰቦችን የሚያንፀባርቁ መሆናቸው የበለጠ እንድማረክ አድርገውኛል የሚለው ቶኒ ዊልያምስ፤ ቀስ በቀስም በሬጌ ሙዚቃ ፍቅር እንደከነፈ ይናገራል፡፡
“ሌሎች ሙዚቃዎችንም እወዳለሁ፤ ግን ለሬጌ ያለኝ ፍቅር ከሁሉም ይልቅብኝ ነበር፡፡ ሬጌ የልብህን ሃሳብ የምትገልጽበት ሙዚቃ ነው፡፡ ቦብ ማርሌይና ሌሎች የሬጌ ሙዚቀኞች በአብዛኛው ዘፈኖቻቸው ውስጥ የመፅሃፍ ቅዱስ  ጥቅሶችን እንደሚጠቀሙ ስረዳ፤ እኔም መፅሃፍ ቅዱስን በጥልቀት ማጥናት ጀመርኩኝ” ብሏል፡፡
ምንም እንኳን ወደ ሬጌ ሙዚቃ የበለጠ እየተሳበ ቢመጣም ነጭ በመሆኑ ራስታ እሆናለሁ ብሎ አስቦ እንደማያውቅ ይናገራል፡፡ “ፀጉሬን ማሳደግ፤ሬጌ ሙዚቃ መጫወት፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ በራስ ተፈሪያኒዝም አስተሳሰብ መመራትን ፈጽሞ አስቤው አላውቅም ነበር፡፡›› በማለትም የህይወቱ አቅጣጫ እንዴት ሳያውቀው እንደተለወጠ ያስረዳል፡፡
በራስ ተፈራይ እምነት በኩል ወደ ሬጌ
ቶኒ በሬጌ ሙዚቃ አድማጭነት ብቻ ተወስኖ አልቀረም፡፡ ስለራስ ተፈሪያኒዝም እምነት የማወቅ ጉጉት አደረበት፡፡ በ1989 እ.ኤ.አ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለ፣ በካሊፎርንያ ግዛት የተከሰተው ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ፣ ህይወት ድንገት ሳይታሰብ ሊቀጭ እንደሚችል ትምህርት እንደሰጠው ያስታውሳል፡፡ ‹‹የመሬት መንቀጥቀጡ ከባድ ስለነበር እንደብዙዎቹ ተማሪዎች እኔም በፍርሃት ራድኩኝ። በዚያ አጋጣሚ ብዙ ነገር ተማርኩ፡፡ በድንገተኛ የተፈጥሮ አደጋ ህይወት በአጭሩ እንደሚቀር ሳስብ ስለ ነፍሴ ደህንነት  እጨነቅ ያዝኩኝ፡፡ ከአሰቃቂ አደጋና መከራ ከሞላበት ህይወት የሚያድነኝን አምላኬን እፈልግም ጀመር፡፡›› ሲል እንዴት ወደ እምነት እንደገባ ያስረዳል፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን በካሊፎርንያ የራስ ተፈራይ እምነት ድርጅት ዋና ፅህፈት ቤት ግቢ ውስጥ  በተዘጋጀ ስብሰባና የሙዚቃ ድግስ ላይ የተገኘው ከጓደኛው ጋር ነበር፡፡ ዊልያምስ ስብሰባውንና ድግሱን ለመታደም ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች አያሌ ሰዎች መሰባሰባቸውን ሲመለከት በእጅጉ ተገረመ፡፡ ይህን ሁሉ የሰው ዘር አንድ ያደረገ እምነትን በቅጡ ማወቅ አለብኝ ብሎ ለራሱ ቃል ገባ፡፡
ከዚያም የመፅሃፍ ቅዱስ ውይይቶች በሚደረጉባቸው ቀናት ሁሉ ዋና ፅህፈት ቤቱን መጎብኘት ሥራዬ ብሎ ተያያዘው፡፡ ጥቁርና ነጭ፣ አፍሪካዊና እስያዊ ሳይባል ሁሉም በአንድ ግቢ መሰባሰቡ ልዩ ስሜት እንደፈጠረበት ቶኒ ያስታውሳል። ስለ ራስተፈርያኒዝም እንዲሁም ስለ “ትዌልቭ ትራይብስ ኦፍ እስራኤል” ብዙ አጠና፤ ብዙ ተመራመረ፡፡  ግን የእምነት ተቋሙን  ከመቀላቀሉ በፊት በቀጥታ ለአምላኩ ፀሎት ማድረግ ነበረበት፡፡ “አምላኬ ትክክለኛ የህይወት አቅጣጫ እከተል ዘንድ እርዳኝ፤ በእምነቴ እፀና ዘንድ ብርታት ስጠኝ” ብዬ ፀሎት አደረግሁ፡፡ ከዚያ ለልቦናዬ የሚሆን መልስ በማግኘቴ ሙሉ እምነት አድሮብኝ የእምነት ተቋሙን  ተቀላቀልኩ፡፡›› ብሏል፡፡ ያን ጊዜ ዊልያምስ የ17 ዓመት ታዳጊ ነበር፡፡ የራስተፈርያን ድርጅት ዋና ቅጥር ግቢ ውስጥ በየጊዜው የሙዚቃ ዝግጅቶች ይካሄዱ ስለነበር እግረመንገዱንም ከሬጌ ሙዚቃ ስልቶች ጋር በስፋት የመተዋወቅ ዕድል ፈጠረለት፡፡ በዚያው ሙዚቃ ወደ ሙያ ገባ፡፡
የመጀመርያዎቹ ሁለት አልበሞች
‹‹ዲል ዊዝ ሪያሊቲ›› የተሰኘውን የበኩር አልበሙን ያወጣው በ2001 ዓ.ም ነበር፡፡ ከዚያም ወደ ጃማይካ በመጓዝ እዚያው መኖር የጀመረ ሲሆን ከእነ ሲዝላ ካከሌንጂ፣ ኬን ቡዝ፣ ሹገር ሚኖት፣ ሞርጋን ሄሪቴጅና ከሌሎች እውቅ የሬጌ ዘፋኞችና ባንዶች ጋር ለረጅም ጊዜ በመስራት ሙያዊ ልምዱን ማበልፀግ እንደቻለ ይናገራል፡፡
በ2009 እ.ኤ.አ ለገበያ ያበቃው ሁለተኛ የሙዚቃ አልበሙ ‹‹ሲምፕል ቲንግስ›› ይሰኛል፡፡ ይህን አልበሙን ለመስራት 25ሺ ዶላር (ግማሽ ሚሊዮን ብር ገደማ መሆኑ ነው) የፈጀበት ሲሆን በታዋቂዎቹ የጃማይካ የሬጌ ሙዚቃ ስቱዲዮዎች (ኪንግስተን፣ ታፍጎንግ ፣ ቦቢ ዲጂታል) እንደተቀረፀለት ይናገራል፡፡
ታዋቂ የጃማይካ ሬጌ ሙዚቀኞች በአልበሙ ላይ በአጃቢነት በመሳተፋቸው ስኬታማ አልበም ለማውጣት ችያለሁ ብሏል ዊልያምስ፡፡ በ1999 እ.ኤ.አ “ሪም ሾት” የተባለ የሙዚቃ ባንድ መመስረቱን የሚናገረው አርቲስቱ፤ ባንዱን በመምራትና ከታዋቂ የሬጌ ሙዚቀኞች ጋር በመጣመር በኒውዮርክ፣ በኒውዝላንድ፣ በጃማይካ፣ በጀርመንና በእንግሊዝ የሙዚቃ ሥራዎቹን እንዳቀረበ ጠቁሟል፡፡ በመላው ዓለም ከሰራቸው ኮንሰርቶች ሁሉ በ2003 ዓ.ም በካረቢያን አገራት:- ጃማይካ፣ በርባዶስ፣ ግሬኔዳና ትሪንዳንድ ቶቤጎ ላይ ያቀረባቸው ኮንሰርቶች ልዩና ስኬታማ እንደነበሩ ያስታውሳል፡፡ በእነዚህ ስኬታማ ኮንሰርቶች ላይ ከእነ ኬን ቡዝ፣ ፍሬድ ሎክስ፣  ጄንትልመን እና ሌሎች እውቅ የሬጌ ሙዚቀኞች ጋር አቀንቅኗል፡፡
የሬጌ ሙዚቃ ንጉስ ቦብ ማርሌይን ጨምሮ እነ ጋርኔት ሲልክ፣ ዴኒስ ብራውን፣ ላኪ ዱቤና ጄንትልመን አርአያዎቹ እንደሆኑ ዊልያምስ ይናገራል። ጆኒ ካሽና ቦብ ዲላን ደግሞ  ከሚያደንቃቸው ሙዚቀኞች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ “ሪምሾት” ከተባለው ባንዱ ጋር ከ20 በላይ ዘፈኖች መስራቱን የሚናገረው አርቲስቱ፤ ከባንዱ ጋር ለሰባት አመታት ከሰራ በኋላ አባላቱ ተበታትነው ባንዱ መፍረሱን ጠቁሟል። ሆኖም ኢትዮጵያ ውስጥ ሙዚቀኞችን አሰባስቦ “ሪምሾት” በሚለው ስያሜ ባንዱን በድጋሚ የማቋቋም ተስፋ ሰንቋል፡፡
ግጥሞቹና የሙዚቃ ፍልስፍናው
ገና በልጅነቱ ግጥም መፃፍ የጀመረው  ቶኒ፤ በሙዚቃ ህይወቱ ከ50 በላይ ኦሪጂናል የዘፈን ግጥሞችን እንደፃፈ ይናገራል፡፡ ‹‹መጀመርያ ላይ እፅፍ የነበረው የግል ስሜቶቼን የሚያንፀባርቁ ግጥሞችን ነበር፡፡ በመጀመርያው አልበሜ ላይ በነባራዊው ዓለም ላይ የማያቸውን ተጨባጭ እውነታዎች የሚያንፀባርቁ ግጥሞችን አቀንቅኛለሁ፡፡ ሰዎች ፍትህ ሲጎድልባቸው፤ መብታቸው ሲጣስ፤ የዘር መድልኦ ሲደርስባቸው አልወድም፡፡ እናም በመጀመርያው አልበሜ ላይ እነዚህን በደሎች በሚያወግዙ፣ ትክክለኛውን የሰው ልጅ አኗኗር በሚያስተምሩ ግጥሞች አመለካከቴን ለመግለፅ ሞክሬያለሁ፡፡›› ብሏል አርቲስቱ፡፡
በሙዚቃ  ስራዬ ስለዓለም የማውቀውን እዘፍናለሁ የሚለው ቶኒ፤ ወደፊት የመፅሃፍ ቅዱስ ትንቢቶችን በጥልቀት መርምሮ በመረዳት፣ ጠቃሚ ሃሳቦችን በሙዚቃው ማንፀባረቅ እንደሚፈልግ ተናግሯል፡፡ ለቤተሰብ የሚስማሙ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑ ዘፈኖችን ደጋግሞ መስራቱን በመግለጽም፤ የሙዚቃዬ ዓላማ ሰዎች በቅን አስተሳሰብ ተቃኝተው ህይወታቸውን እንዲመሩ ማስተማር ነው - ብሏል፡፡
3ኛ የአልበም ስራውን በኢትዮጵያ
ቶኒ ዊልያምስ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ለመኖር የወሰነበት የራሱ ምክንያት አለው፡፡ “ኢትዮጵያን የመረጥኳት መንፈሳዊ መነቃቃትን፤ ወሰን የለሽ ፍቅርና ህብረ-ብሄራዊነት የሞላባት ምድር ስለሆነች ነው›› ባይ ነው፡፡ ለዚህም ነው ከሁለት አመት ወዲህ ስራውንና ኑሮውን በሁለቱ የኢትዮጵያ ከተሞች ያደረገው - በአዲስ አበባና ባህርዳር፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ መኖርና መስራት ሲመኘው የነበረ እንደሆነ ያወሳው አርቲስቱ፤ ‹‹ባክ ቱ ኤደን›› የተሰኘውን ሶስተኛ አልበሙን በኢትዮጵያ ለመስራት መምረጡን ይናገራል፡፡  
አዲሱ አልበሙ የልቡንና የነፍሱን ፈቃድ የሚያሟሉ ዘፈኖች እንደሚካተቱበት ገልጿል፡፡ ዘፈኖቹ በተለያዩ የሬጌ ሙዚቃ ስልቶች የሚቀናበሩ ሲሆን እንደ ክራር ባሉ ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያዎችም ይታጀባሉ ብሏል፡፡ ከኢትዮጵያ የሙዚቃ ባንዶች ጋር አልበሙን እንደሚሰራ የገለፀው አርቲስቱ፤ ጥቁር አንበሳ፤ ቺጌና መሃሪ ብራዘርስ ይገኙበታል ብሏል፡፡ እነ ራስ ስዩም፣ ኢቦኒ፣ ኬኒ አለን፣ የመሳሰሉ ሙዚቀኞች እንደሚያጅቡትም ገልጿል፡፡
በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ለአድማጭ ጆሮ ይደርሳል ተብሎ የሚጠበቀው “ባክ ቱ ኤደን”፤ አልበም፤ በጀርመን፣ በጃማይካና በሌሎች የዓለም አገራት የተቀረፁ ዘፈኖችን የሚያካትት ሲሆን ለኢትዮጵያውያን ባህልና እሴት ያለውን ክብር የሚገልፁ ዘፈኖች እንደሚያቀነቅን አርቲስቱ ገልጿል። “የኔ ፍቅር” የተሰኘው ዘፈኑ አንዱ ነው፡፡ “ባህርዳር” የሚለው ደግሞ በባህርዳር ለተዋወቃት ኢትዮጵያዊት ቆንጆ ውዳሴ የሚያቀርብበት ዜማው እንደሆነ አርቲስቱ ይገልፃል፡፡
“ባድ ኔም” በሚለው ዘፈኑ ደግሞ በራስታዎች የህይወት ፍልስፍናና እምነት ላይ የሚሰነዘሩ አሉታዊ ትችቶችን በመቃወም የሚያቀነቅንበት እንደሚሆን ቶኒ ዊልያምስ ተናግሯል፡፡ መልካሙን ሁሉ እንመኝለታለን።


Published in ጥበብ

“ባለሀገሩ አስጐብኚ ድርጅት” አባት አርበኞችን ወደ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ወስዶ ለማስጐብኘት እየተንቀሳቀሰ ነው
“ግድቡን ጠዋት ጐብኝቼ ማታ ብሞት ገነት እንደምገባ እርግጠኛ ነኝ” - አባት አርበኛ
ትክክለኛ ስሙ ተሾመ አየለ ቢሆንም ብዙዎች “ባለሀገሩ” በሚል ስያሜው የበለጠ ያውቁታል፡፡ ዘወትር በሚለብሰው ባህላዊ ልብስና በሚያጎፍረው ፀጉሩ ይታወቃል። በድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) “ጥቁር ሰው” የሙዚቃ ቪዲዮ ላይ የባልቻ አባነፍሶን ገፀ-ባህሪ ወክሎ በመጫወት ብዙዎችን አስደምሟል። “ባላገሩ” የተሰኘ የአገር ውስጥ አስጐብኚ  ድርጅት ከፍቶ በመስራት ላይም ይገኛል። በቅርቡ በቶቶት ሆቴል በተዘጋጀ የባህል ልብሶች የመልበስ ውድድር ከተሸላሚዎቹ አንዱ ሆኗል - ወጣት ተሾመ አየለ፡፡
ባለፈው ማክሰኞ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ፤ 50 ለሚሆኑ አርበኞች የታላቁን ህዳሴ ግድብ ለማስጎብኘት ማቀዱን ተናግሯል፡፡
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ በቱሪዝም፣ በሥራ ተመክሮውና በህይወቱ ዙርያ አነጋግራዋለች፡፡

ባላገር ነኝ፤ ንግግር አልችልም ስትል ሰምቼ ነበር፡፡ ትውልድና እድገትህ የት ነው?
ትውልድና እድገቴ በሰሜን ሸዋ አካባቢ፣ ደብረ ብርሃን ዙሪያ፣ ወረዳ በዞ የሚባል ቀበሌ ውስጥ ነው።
እንዴት ወደ አዲስ አበባ መጣህ? የትምህርትህስ ሁኔታ ምን ይመስላል?
ትምህርቴን የተማርኩት እስከ 10ኛ ክፍል ነው። ነገር ግን አሁን በምሰራበት የቱሪዝም ሙያ ዙሪያ የተለያዩ የቱሪዝም ስልጠናዎችን ወስጃለሁ፡፡ አዲስ አበባ ከገባሁ ወደ 12 ዓመት ሆኖኛል፡፡ አዲስ አበባ መጥቼ ስራ የጀመርኩት በጣም አነስተኛ በሚባል ደሞዝ ነበር፡፡
አነስተኛ ስትል ስንት ብር ነው? ስራውስ ምን ነበር?
ደሞዙ በወር 35 ብር ሲሆን ስራው ዘበኝነት ነበር። ማታ ዘበኝነት እሰራለሁ፤ ቀን ቀን ደግሞ የጉልበት ስራ፣ ሸክም እየተሸከምኩ  መንጃ ፍቃድ ለማውጣት ገንዘብ እቆጥብ ነበር፡፡ ቁርስ በልቼ ከሆነ ምሳ ወይም እራት በመዝለል ነበር ገንዘብ የምቆጥበው፡፡ ያንን ካላደረግሁ ትልቅ ቦታ እንደማልደርስ አውቅ ነበር። ህይወት እንደጠበቅኩት ባለመሆኑ እንጂ አዲስ አበባ የመጣሁት ለመስራት ሳይሆን ለመማር ነበር፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ግን መማር አልቻልኩም፡፡
መንጃ ፍቃዱን አወጣህ?
የእግዚአብሄር ፈቃድ ተጨምሮበት እኔም ታግዬ መንጃ ፈቃዴን አወጣሁ፡፡ በቢጂአይ ኢትዮጵያ በቢራ ጫኝ እና አውራጅነት ተቀጥሬ እሰራ ነበር። በኋላ ላይ መንጃ ፈቃድ ስለነበረኝ  በሹፍርና ተቀጠርኩ፡፡ ከዚያ የሽያጭ ባለሙያ ሆንኩኝ፡፡
ለምንድነው ብዙ ሰዎች “ባላገሩ” እያሉ የሚጠሩህ?
ስራዬን በአግባቡ ስለምሰራ አለቆቼ ይወዱኝ ነበር፡፡ ታዲያ አብረውኝ የሚሰሩት ባልደረቦቼ “ይሄ ቆምጬ ባላገር እኮ እኛን አሳጣን” ይላሉ፡፡ በዚያው ባላገር እያሉ መጣራት ጀመሩ፡፡ እኔም አልከፋኝም። እውነትም ባላገር ነኝ፡፡ ባላገር ማለት አገር ያለው ማለት ነው፡፡ “ትናንትና ከእረኝነት መጥቶ ዛሬ እኛን በለጠን፤ ይሄ ባላገር ዶሮ ጠባቂ” ይሉኝ ነበር።  ባላገር ማለት ወግ ማእረግን አክብሮ የሚኖር፤ የሚታረስ ቦታ፣ የሚኖርበት ስፍራ፣ የሚከበርበት ባህልና ትውፊት ያለው ማለት ስለሆነ፣ ባላገርነቴን ተቀብዬው ኮርቼበት እኖራለሁ፡፡ በአጠቃላይ ባላገር ማለት በእርሻ አገሩን አልምቶ፣ አገሩን የሚመግብ የአገር ዋልታ ማለት ነው፡፡
እንዴት ነው ወደ ቱሪዝም ዘርፍ ልትገባ የቻልከው? “ባላገሩ አስጎብኚ” ድርጅትን እንዴትና መቼ አቋቋምክ?
ወደ ቱሪዝም ሥራ ለመግባት አጋጣሚው የተፈጠረልኝ በ1997 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ነው፡፡ የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ በተካሄደበት ወቅት የዘመዴን መኪና የሊቢያ ኤምባሲ ተከራይቶት ሰለነበር እሱ ላይ እሰራ ነበር፡፡ በወቅቱ እኔ የማውቃቸው የእንግሊዝኛ ቃላት ቢቆጠሩ 15 አይሞሉም ነበር፡፡
እስከ 10ኛ ክፍል ተምረህ የለም እንዴ? እንዴት 15 አይሞሉም፤ ቢያንስ 150 እንኳን መሆን ነበረባቸው …
(ሳ….ቅ) ያው ትምህርት አቋርጠሽ ለረጅም ጊዜ ሌላ ስራ ስትሰሪም ይረሳል እኮ! የሆኖ ሆኖ እዚያ ስሰራ የቱር ባለቤቶች ሸራተን አገኙኝ፡፡ መኪናውንም ወደዱት፤ መከራየት ጀመሩ፡፡ ያለኝን የስራ ፍቅር፣ ትህትናዬን ያዩ የኤፍኬ አስጎብኚ ድርጅት ባለቤት አቶ ፍቅረሥላሴ፤ “ለቱሪዝም የሚመጥን ባህሪ ስላለህ ከዚህ ሥራ ባትወጣ ጥሩ ነው” የሚል ምክር ሰጡኝ። ከዚያም በራሳቸው ድርጅት ስልጠና ሰጥተውኝ፣ ባዶ መኪና ይዤ፣ ቱሪስቶች ተከትዬ እየሄድኩ ልምድ እንዳዳብር ካደረጉኝ በኋላ፣ ብቃቴን አረጋግጠው ከእሳቸው ጋር ለረጅም ጊዜ ሰራሁ፡፡ ከዚያም ለውጥ ስለሚያስፈልግ በሌላ ድርጅት ውስጥ ተቀጠርኩ። ከሁለት ዓመት በፊት ደግሞ “ባላገሩ አስጎብኚ” በሚል የአገር ውስጥ ጎብኚዎች ላይ ትኩረት ያደረገ የራሴን ድርጅት ለመክፈት በቃሁ፡፡
በምን ያህል በጀት ነው ድርጅትህን የከፈትከው?
ምንም ገንዘብ አልነበረኝም!! በሶስትና አራት ድርጅቶች ተቀጥሬ የቱር ስራ ስሰራ የቆጠብኩት ገንዘብ አልነበረኝም፡፡ በነገራችን ላይ ቱሪዝም ማለት ለእኔ ፍቅር ነው፤ ህይወትሽን ሰጥተሸ ልትሰሪው የሚገባ ስራ ነው፡፡ ገጠር ውስጥ እንግዳ ሲመጣ ጎንበስ ቀና ብለሽ፣ እግር አጥበሽ፣ ቤት ያፈራውን አቅርበሽ፣ ፊትሽን በፈገግታ አድምቀሽ ነው የምትቀበይው፡፡ ይሄ ቱሪዝም የሚፈልገው ትክክለኛ ባህሪ ነው፡፡ ይህ ባህሪ ደግሞ በትምህርት ሳይሆን በአስተዳደግና ካደግሽበት ማህበረሰብ የምትወርሺው ነው፡፡ በዲግሪ በማስተርስ ይመጣል ብዬ አላስብም፡፡ የሆነ ሆኖ ብር ያላጠራቀምኩበት ዋና ምክንያት፣ ልናስጎበኝ ስንሄድ የምወስዳቸው እንግዶች ቢታመሙ፣ አንድ ነገር ቢደርስባቸው በቅርብ ለመገኘት ስል እነሱ የሚያርፉበት ውድ ሆቴል  ስለማድርና አበሌን ለሆቴልና ለምግብ ከፍዬ ባዶ እጄን ወደ ቤቴ ስለምመለስ ነበር፡፡
ታዲያ አስጎብኚ ድርጅትን ያህል ትልቅ ተቋም በምን ካፒታል ከፈትክ?
በመጨረሻ ላይ የሰራሁበት ድርጅት አንድ መኪና ተበላሽቶብኝ ከስራ ስቀነስ፣ በባንክ ሂሳቤ የነበረኝ ገንዘብ 1842 ብር ብቻ ነበር፡፡ ይህን ብር ይዤ ነው “ባለሀገሩ አስጎብኚ” ድርጅትን የከፈትኩት፡፡ ከተቋቋመ ሁለት አመቱ ነው፤ ስራውን አውቀዋለሁ፤ ፍቅር የሆነ ስራ ነው፤ ስራውን ስትሰሪ ሆቴሎች ታውቂያለሽ፤ ብዙ ግንኙነት ትፈጥሪያለሽ፤ ስለዚህ በዱቤ መስራት ይቻላል። ብድርም ታገኚያለሽ፡፡ ለስራዬ ስኬት ባለቤቴ፣ እህቶቼና አጎቴ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርገውልኛል፡፡ ገንዘብ አበድረውኛል፡፡ አዲ ብድርና ቁጠባም ወደ 300 ሺህ ብር ገደማ አበድሮኛል፡፡ አምስት ቋሚና 18 ገደማ የኮሚሽን ሰራተኞች አሉት፤ ድርጅቱ፡፡ ትኩረት ያደረግነው ሎካል ቱሪዝም (የአገር ውስጥ ጐብኚዎች) ላይ ነው፡፡ በአገራችን አገርን የመጎብኘት ባህላችን ደካማ በመሆኑ ሳዝን ኖሬያለሁ፡፡ አሁን ግን ትኩረት ያደረግነው ዜጎች ስለአገራቸው በደንብ እንዲያውቁና እንዲጎበኙ ማድረጉ ላይ ነው። ኢትዮጵያን ለነጭ ጎብኚዎች ትተን መቀመጥ የለብንም፡፡ እነሱም አጠራቅመው እንጂ ተርፏቸው አይደለም የሚጐበኙት፡፡
በአሁኑ ወቅት አንድ ሰው ሁለት ማኪያቶ የሚጠጣ ከሆነ አንድ እየጠጣ፣ የተወሰነ መንገድ በእግሩ በመሄድ የትራንስፖርት ወጪውን ቀንሶ፣ በቀን አስር ብር፣ በወር 300 ብር፣ በአመት 3600 ብር በመቆጠብ፣ በጋራ ሰብሰብ ብሎ አገርን የመጎብኘት ልምድ እንዲያዳብር ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እየሰራን ነው፡፡
በሁለት አመት ውስጥ ምን ያህል የአገር ውስጥ ጎብኚዎችን አስተናግዳችኋል?
ባለፈው አመት 1ሺህ ዘጠኝ መቶ ጐብኚዎችን አስተናግደናል፡፡ ዘንድሮም ተቀራራቢ ቁጥር ያላቸው የአገር ውስጥ ጎብኚዎች ያስተናገድን ሲሆን አሁን የውጭ ጎብኚዎችንም ማስተናገድ ጀምረናል። ግንኙነቶችን እየፈጠርን ነው፡፡ ፍላጎት እያሳዩ ያሉ ጎብኚዎች አሉ፡፡ ሶስት ጥሩ ጥሩ የጉዞ መኪኖችም አሉን፡፡
ወደ አለባበስህ እንምጣ፡፡ 365 ቀናት የአገር ባህል ልብስ ነው የምትለብሰው፡፡ ፀጉርህን እንደ አርበኞች አጎፍረህ በማበጠርም ትታወቃለህ፡፡ መቼ ነው የጀመርከው?
ተወልጄ ያደግሁት ገጠር እንደመሆኑ፣ አዲስ አበባ እስክመጣ በባህል ልብስ ነው ያደግሁት፡፡ አዲስ አበባ ከመጣሁ በኋላ አጎቴና እህቶቼ የገዙልኝ ዘመናዊ የፈረንጅ ልብስ ከሰውነቴ ጋር ሊዋሀድ አልቻለም፡፡ ሱፍ ለብሼ አየሁት፤ አልተስማማኝም፣ ጂንስ ለበስኩኝ፤ መራመድ አልቻልኩም፡፡ ስለዚህ ለእኔ የተፈጠረ አይደለም አልኩና ወደ አሳደገኝ ቁምጣዬ ተመለስኩኝ፡፡ ከተወለድኩ ጀምሮ እስካሁን በአገሬ ባህል ልብስ ነው የምዋበው፤ የፈረንጅ ልብስ ለብሼ አላውቅም፤ የመልበስ ፍላጎትም የለኝም፡፡
አርበኞችን ወደ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ወስዶ የማስጎብኘት ሀሳብ የተጠነሰሰው እንዴት ነው?
እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገራት ብቸኛዋ ቅኝ ያልተገዛች አገር ናት፡፡ በዚህም እንኮራለን፡፡ ለዚህ ኩራታችን ዋነኛ ባለውለታዎች ደግሞ የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ናቸው፡፡ ለዚህ ኩራት፣ ነፃነትና ክብር ህይወት አልፏል፤ ደም ፈስሷል፤ አጥንት ተከስክሷል፡፡ በአንድ አጋጣሚ አንድ አባት አርበኛ ያገኙኝና “አሁን 94 አመት ሆኖኛል፤ በተለያየ ጊዜ የነበሩ ትውልዶች የተለያየ ገድል ሰርተው አልፈዋል፤ ይሄኛው ትውልድ ደግሞ የዘላለም ቁጭቴ የነበረውን የአባይን ግድብ እየገነባ ነው፡፡ እኔ ግድቡን ጠዋት ጎብኝቼ ማታ ወይም
በነጋታው ብሞት ቀጥታ ገነት እንደምገባ እርግጠኛ ነኝ፤ እህ የእኔ ልጅ፤ ይህን ብታደርግ አንተንም መርቄህ አልፋለሁ” አሉኝ፡፡ ጉዳዩን ከስራ ባልደረቦቼ ጋር ተመካክረንበት፡፡ ለምን በመኪና የምንችለውን ያህል ወስደን አናስጎበኛቸውም የሚል ሀሳብ ላይ ደረስን፡፡ ከዚያም ከጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ጋር ተነጋገርን፤ ሀሳቡ ጥሩ ነው በሚል ድጋፍ ሰጡን፡፡ መጀመሪያ በኛ ደርጅት የሚሳካ መስሎን ነበር፡፡ በትንሹና በህፃኑ ድርጅታችን የምንሰራው ከሆነ ግንጥል ይሆናል በሚል፣ ጉዳዩ አገራዊ ይዘት እንዲኖረው ለማድረግ ወሰንን፡፡
በመግለጫው ላይ እንደተባለው ወደ 77 ያህል ተጓዦች ይሳተፋሉ፤ በጀቱም ወደ አንድ ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ነው፡፡ በእርግጠኛነት የሚሳካ ዕቅድ ይመስልሃል?
እኛ እንዲሳካ የሚቻለውን ሁሉ እናደርጋለን። በሄሊኮፕተር ወስደን ብንመልሳቸው መልካም ነው። ይሄ እንግልትን ይቀንሳል፡፡ ምክንያቱም ትንሹ እድሜ የሚባለው 85 ዓመት ነው፡፡
ሁሉም ከዚያ በላይ እስከ 96 ዓመት እድሜ ያላቸው ናቸው፡፡ እነዚህ አባቶች ዶክተርና ነርሶች አብረዋቸው የሚጓዙ ቢሆንም እንግልቱን መቀነስ አለብን፡፡ በአንድ ቀን ግድቡን ጐብኝተው በዚያው ቀን ቢመለሱ ይሻላል፡፡ ለዚህም ሄሊኮፕተር የምንከራይበትን አሊያም በነፃ የምናገኝበትን መንገድ እየፈለግን ነው፡፡
እስካሁን ድጋፍ ለማድረግ ፈቃዳቸውን ያሳዩ ድርጅቶች አሉ?
ለኢትዮጵያ አየር መንገድና ለመከላከያ ሚኒስቴር ደብዳቤ ፅፈን ተስፋ ሰጪ ነገሮችን አይተናል፡፡ የትኛውም ኢትዮጵያዊ ካለው ላይ ቀንሶ በመስጠት፣ የአርበኞችን ምኞት እውን ያደርግልናል የሚል ተስፋ አለን፡፡ የአባቶች ወደ አባይ መሄድ፣ እዚያ በበረሀ ግድቡን በፅናት  የሚሰሩ ኢትዮጵያዊያንን ሞራል ይገነባል፡፡ አባቶችም ምርቃት ይሰጣሉ። አባቶች ከጉብኝት በኋላ አዲስ አበባ ተመልሰው ምስክርነት ሲሰጡ ህዝቡ ለግድቡ ብር የማዋጣት ፍላጎቱ ይጨምራል፡፡ የአንዳንድ “አማርኛ ተናጋሪ ግብፃዊያንንም” አንገት ያስደፋል፡፡ እስከ መጪው መስከረም ሶስት ድረስ የጉብኝት ጉዞው በትክክል እንደሚሳካ እምነቴ ነው፡፡ እስካሁን በእጃችን የገባ ገንዘብ የለም፡፡ ግን ይሳካል፡፡
በመግለጫህ ላይ 77 ተጓዦች በጉብኝቱ እንደሚካተቱ ገልፀሃል፡፡ እነማን ናቸው?
50 አርበኞች፣ 16 የተለያዩ ሚዲያ ጋዜጠኞች፣ 6 ከአባቶች የአደራ ቃል የሚረከቡ የመንግስት ባለስልጣናት፣ አንድ ዶክተርና አንድ ነርስ፣ ሁለት አዝማሪዎች፣ ሁለት አስተባባሪዎች፣ በድምሩ 77 ተጓዦችን ያካትታል፡፡

Page 5 of 16