በአብዛኛው የፖለቲካ መሪዎች ስኬትና ውድቀት የተመሰረተው በሚያከናውኗቸው ተግባራት ብቻ ሳይሆን ከአንደበታቸው በሚሰነዝሯቸው ቃላትም ጭምር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዚህም የተነሳ የፖለቲካ መሪዎች ከመናገራቸው በፊት ሁለት ሶስቴ ማሰብና ንግግራቸው ሊፈጥር የሚችለውን ስሜት በቅጡ ማገናዘብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተቻለ መጠንም ራሳቸውን ከአፍ ወለምታ መጠበቅ ይገባቸዋል፡፡
በፈረንሳይ ብሄራዊ ግንባር (Front Nationale) የተሰኘውን የፈረንሳይ አክራሪ ብሄርተኛ የፖለቲካ ፓርቲ በመመስረት የሚታወቁትና በጥቁሮች፣ በስደተኞች አይሁዳውያንና በሮማዎች ላይ ባላቸው ከፍተኛ ጥላቻና የዘረኝነት አቋም በፈረንሳይ ብቻ ሳይሆን በምድረ አውሮፓ ስማቸው የናኘው ዦን ማሩ ለፔን፤ ባለፈው ሳምንት አይሁዳውያንን በተመለከተ ያደረጉት ንግግር ከፍተኛ አቧራ አስነስቷል፡፡
ንግግራቸው ያነጣጠረው ቁጥራቸው በርከት ያለ አይሁዳውያን በተካተቱበት የፈረንሳይ አርቲስቶች ቡድን ላይ ሲሆን ለሰነዘሩት ክፉ ንግግር ሰበብ የሆናቸውም የብሔራዊ ግንባር ፓርቲያቸው በቅርቡ በተካሄደው የአውሮፓ ፓርላማ ምርጫ የተቀዳጀውን ከፍተኛ ውጤት የአርቲስቶች ቡድኑ ተቃውሞ በማውገዙ ነው። አዛውንቱ ፖለቲከኛ ባቀረቡት ንግግር፤  “በሚቀጥለው ጊዜ ለእነዚያ ይሁዲ የአርቲስት ጥርቃሞዎች ሰፋ ያለ ምድጃ እናዘጋጅላቸዋለን፡፡ ለአሁኑ ግን በዚህ ምጣድ የምጠብሰው አንድ ይሁዲ ዘፋኝ እፈልጋለሁ!” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
እኒህ ነውጠኛ የፖለቲካ መሪ፤ በዚህ እጅግ ዘረኛ ንግግራቸው ስለምድጃ ያነሱት በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት በናትዚ ጀርመን እጅ ወድቀው በጋዝ ታፍነው ከተገደሉ በኋላ በትልቅ የማቃጠያ ምድጃ ተቃጥለው ያለቁበትን ሁኔታ ለመጠቆምና አሁንም ለአይሁዶች የሚገባው ቅጣት ይህ ነው ለማለት ነው። ዦን ማሪ ለፔን፤ በዘረኝነታቸውና በልቅ አንደበታቸው የታወቁ ቢሆንም ጠንካራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አቅም ባላቸው ፈረንሳይ ይሁዲ ማህበረሰቦች ላይ የሰነዘሩት የአሁኑ መርዘኛ ንግግር ያስነሳው የፖለቲካ እሳት ግን እንዳለፉት ጊዜያት በቀላል ውግዘትና ተቃውሞ ብቻ የሚያልፍ አልሆነም፡፡ ይልቁንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፈረንሳይ የፖለቲካ መድረክ የተሻለ ተቀባይነትና ድጋፍ እያገኘ የመጣውን የብሄራዊ ግንባር ፓርቲ ከስሩ የሚነቀንቅ ሆኗል፡፡ በአክራሪ ብሄርተኛ የፖለቲካ አቋሟና በዘረኝነቷ ከአባቷ ተለይታ የማትታየው የፓርቲው ሊቀመንበር ማሪን ለፔን እንኳን ንግግሩ በፓርቲው ህልውናና የወደፊት እንቅስቃሴ ላይ የደቀነው ከፍተኛ አደጋ በግልጽ ታይቷታል፡፡ ስለዚህም አደጋውን ለመከላከል ስትል በአባቷ ላይ እንድትነሳ ተገደደች፡፡  እናም፤ ማሪን ለፔን አደባባይ ቆመችና እንዲህ አለች:- “የፈረንሳይ አይሁድ ማህበረሰብን በተመለከተ አባቴ እንዲያ ያለ ንግግር በመናገሩ ከፍተኛ የፖለቲካ ስህተት ፈጽሟል፡፡”
ይህን የሰሙት ሽማግሌው አባቷ ዦን ማሩ ለፔን ግን ስህተታቸውን አምነው ለመቀበል ጨርሶ አልፈለጉም። ይልቁንም “ለዚህ ያበቃኋት ልጅ በእኔ ላይ ከፍ ያለ ክህደት በመፈፀም ከጀርባዬ ወግታኛለች” በማለት ተቃውሞአቸውን ገለፁ፡፡
ዦን ማሪ ለፔን በዚህ ብቻ አላበቁም፡፡ ባለፈው አርብ የብሄራዊ ግንባር ፓርቲ አባላትንና ደጋፊዎችን ሰብስበው “ጎበዝ! በጠንካራ ብሄርተኛ አቋሙ የታወቀውን ፓርቲያችንን ወደ ተራና አጨብጫቢ ፓርቲነት እንዲቀየር በማድረግ አመራሩ ትልቅ የፖለቲካ ስህተት እየፈፀመ እንደሆነ ልብ በሉልኝ!” በማለት በተፈጠረው የፖለቲካ እሳት ላይ ነዳጅ ጨምረው ይበልጡኑ አጋጋሉት፡፡ፈረንሳውያን አሁን በጉጉት እየጠበቁት ያለው ልጅት ማሪን ለፔን በፓርቲዋ ላይ እየነደደ ያለውን እሳት እንዴት እንደምታጠፋው ለማየት ነው፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

“ግብረ ሰዶማውያን
በድንጋይ ተወግረው መሞት አለባቸው”
የተለያዩ የአለማችን ሀገራት እንደሚከተሉት የፖለቲካ ስርአት በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የተለያየ አቋም ያራምዳሉ፡፡ ለምሳሌ የግብረ ሰዶማዊነትን ጉዳይ በተመለከተ ለአሜሪካና ለአውሮፓ መንግስታት ነገሩ የዜጎች ሰብአዊ መብት ጉዳይ ሲሆን ለአብዛኞቹ የአፍሪካ መንግስታት ደግሞ ምንም አይነት ተቀባይነት የሌለው የወንጀል ድርጊት ተደርጎ ይቆጠራል፡፡
ከጥቂት ወራት በፊት የኡጋንዳ መንግስት ግብረ ሰዶማዊነት በወንጀል የሚያስቀጣ የተከለከለ ድርጊት መሆኑን የሚደነግግ ህግ አውጥቶ በስራ ላይ አውሏል፡፡ በፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ የሚመራው የኡጋንዳ መንግስት፣ ይህን ህግ በማውጣቱ የተነሳ ከአሜሪካና ከበርካታ የአውሮፓ መንግስታት እንዲሁም ከሌሎች የመብት ተሟጋች ነን ከሚሉ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የዜጎቹን ሰብአዊ መብት ጥሷል ወይም አላስከበረም በሚል ያልተቋረጠ የውግዘት ናዳ ወርዶበታል፡፡
በተለይ የአሜሪካ መንግስት በቅርቡ ባወጣው መግለጫ፤ የኡጋንዳ መንግስት ግብረ ሰዶማዊነትን በመከልከል ያወጣውን ህግ ባስቸኳይ ካልሰረዘ ማዕቀብ እንደሚጣልበት አስጠንቅቋል፡፡ ባለፈው ሳምንት ግን ከአሜሪካ ኦክላሆማ ግዛት ግብረ ሰዶማዊነት በተመለከተ አንድ ለየት ያለ ነገር ሲነገር ተደምጧል፡፡ ለአክላሆማ ከተማ ምክር ቤት ምርጫ የቲ ፓርቲን ወክለው የሚወዳደሩት ስኮት ኤስክ፤ ግብረ ሰዶማዊነትን መቃወም ብቻ ሳይሆን ግብረ ሰዶማውያን የሆኑ ሁሉ የብሉይ ኪዳን መጽሀፍ ቅዱስ አስርቱ ትዕዛዝ እንደሚደነግገው በድንጋይ ተወግረው እንዲገደሉ እንደሚፈልጉ በምረጡኝ ቅስቀሳቸው ወቅት በግልጽ አሳውቀዋል፡፡
የሮማ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ በቅርቡ ግብረ ሰዶማዊነትን በተመለከተ “ግብረ ሰዶማውያንን ለመተቸትና በእነሱ ላይ ለመፍረድ እኔ ማን ነኝ?” በማለት የሰጡትን መግለጫ በተመለከተም ስኮት ኤስክ በፌስቡክ ገፃቸው ስለ ግብረሰዶም አስፀያፊነት በመጽሀፍ ቅዱስ የተፃፈውን በመጥቀስ፣ ለግብረ ሰዶማውያን የሚገባው ቅጣት በድንጋይ ተወግሮ መሞት እንደሆነ በማስፈር ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ይሄ የምርጫ ቅስቀሳ ንግግር የተደመጠው ከአሜሪካዋ ግዛት ከኦክላሆማ መሆኑ ብዙዎችን በግርምታ አፍ አሲዟል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ
Saturday, 12 July 2014 12:44

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቅሌት

    መንግስታት ከምንጊዜውም በበለጠ ቅሌት ውስጥ የሚዘፈቁበት ጊዜ አለ ከተባለ በምርጫ ወቅት ነው። የየሀገሮቻቸው ብሄራዊ የምርጫ ጊዜ ሲቃረብ ጀምሮ እስከሚጠናቀቅበት ጊዜ ድረስ መንግስታት የማይሰሩት ቅሌት የለም፡፡ አንዳንዱ መንግስት ያሰጉኛል የሚላቸውን ተፎካካሪዎቹን እዚህ ግባ የማይባል ሰበብ አስባብ በመፍጠር ከያሉበት ለቃቅሞ ወህኒ ያጉራል፡፡
አንዳንዱ መንግስት ደግሞ ተቃዋሚዎቹን ብቻ ሳይሆን ጋዜጠኞችንም ጨምሮ ያስራል፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ግንባር ቀደም ተፎካካሪያቸውን ብቻ ለይተው ከጨዋታ ውጭ የሚያደርግ ኮሚክ የምርጫ ህግ ያወጣሉ፡፡ ለምሳሌ የምያንማር (በርማ) ወታደራዊ ደርግ በ2008 ዓ.ም ያወጣው የምርጫ ህግ፣ የውጪ ሀገር ዜጋ ባል ያላቸው በርማውያን ፖለቲከኞች ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫ መወዳደር እንደማይችሉ ይደነግጋል፡፡
ይህ አስቂኝ የምርጫ ህግ ለየትኛው ፖለቲከኛ ተብሎና የትኛውን ፖለቲከኛ ከምርጫ ጨዋታ ውጭ ለማድረግ ታስቦ እንደወጣ በጣም ግልጽ ነው። በሚቀጥለው አመት በምያንማር በሚደረገው ምርጫ ከፍተኛ የማሸነፍ እድል ያላቸው ዝነኛዋ የነፃነትና የመብት ታጋይ ኦንግ ሳን ሱኪ ብቻ ናቸው። እንግሊዛዊ ባል ያላቸው ፖለቲከኛም ከእሳቸው ውጭ ማንም አልነበረም፡፡ እናም የምርጫ ህጉ ታቅዶና በሚገባም ታስቦበት የወጣው፣ ምርጫውን በቀላሉ እንደሚያሸንፉ የታመነውን ኦንግ ሳን ሱኪን ከጨዋታ ውጪ ለማድረግ ነው፡፡
እንደ ፖላንድ አይነት መንግስቶች የሚሰሩት ቅሌት ደግሞ ትንሽ ረቀቅ ያለ ነው፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ የፖላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ተስክ፤ በሚቀጥለው አመት በሚደረገው ጠቅላላ ምርጫ ፓርቲያቸው “ሲቪክ “ፕላትፎርም” ፓርቲ ማሸነፍ እንዲችል የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትራቸውን ይጠሩና ከወዲሁ አንድ ነገር እንዲያደርጉ ያዟቸዋል፡፡
ምኒስትሩም በጉዳይ ላይ ካሰቡበት በኋላ አሁን ባለው የፖላንድ የኢኮኖሚ ሁኔታ በሀገሪቱ የወለድ መጠን ላይ መጠነኛ ቅናሽ ማድረግ ከተቻለ፣ ገዢው የሲቪክ ፕላትፎርም ፓርቲ በቀጣዩ ምርጫ የተሻለ ድጋፍ ማግኘት እንደሚችል ይገምታሉ፡፡   
ከዚያም ቀጥ ብለው ወደ ፖላንድ ማዕከላዊ ባንክ ዋና መስሪያ ቤት ያመራሉ፡፡ የባንኩ ገዢ ከሆኑት ከማሪክ ቤልካ ጋር እንደተገናኙም ቀጣዩ ምርጫ ከመካሄዱ በፊት በወለድ መጠኑ ላይ መጠነኛ ቅናሽ በማድረግ ገዢው ፓርቲ በምርጫው እንዲያሸንፍ የበኩላቸውን እገዛ እንዲያደርጉ ጥያቄአቸውን ያቀርቡላቸዋል፡፡
የባንኩ ገዢ ማሪክ ቤልካም በበኩላቸው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ተስክ የገንዘብ ሚኒስትሩን ከስልጣናቸው ካባረሩላቸው የተጠየቁትን እንደሚፈጽሙ ለሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ አረጋገጡላቸው፡፡ የጉዳዩ ዝርዝር ሪፖርት የቀረበላቸው ጠቅላይ ምኒስትር ዶናልድ ተስክም ለአፍታም እንኳ ሳያመነቱ ኢኮኖሚውን በወጉ መምራት ተስኖታል የሚል መናኛ ሰበብ በመፍጠር የገንዘብ ሚኒስትሩን ከስልጣኑ አባረሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩና የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህን ሁሉ ነገር የሰሩት በከፍተኛ ጥንቃቄና ምስጢር ነበር፡፡ ሆኖም ግን ባለፈው ሳምንት አንድ ጉድ ወጣ። የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከጠቅላይ ሚኒስትሩና ከማዕከላዊ ባንክ ገዢ ጋር ያደረጉት ንግግር በምስጢር ቴፕ ተቀርፆ ይፋ ወጣ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ተስክም ስልጣን እንዲለቁ ተጠየቁ፡፡ እሳቸው ግን ስልጣን መልቀቁን በጄ አላሉም፡፡ ይልቁንም የሀገሪቱን ርዕሰ መንግስት ንግግር በድብቅ መቅዳት ከመፈንቅለ መንግስት የማይተናነስ ወንጀል መሆኑን በመግለፅ ክስ ለመመስረት እንደሚገደዱ አስጠነቀቁ፡፡ የሌባ ዓይነ ደረቅ…ይሏል ይሄ ነው!!

Published in ከአለም ዙሪያ

አንደኛው የአለም ጦርነት የተጀመረበትና እንግሊዝ ወደ ጦርነቱ የገባችበት 100ኛ ዓመት፣ በመላው እንግሊዝ መብራት በማጥፋት፣ በጨለማ ውስጥ በሚከናወኑ የተለያዩ ኪነጥበባዊ ዝግጅቶችና ፌስቲቫሎች እንዲሁም በዌስት ሚንስቴር አቤይ በሚከናወን የሻማ ማብራት ስነ-ስርዓት እንደሚከበር ቢቢሲ ዘገበ፡፡ በመጪው ነሃሴ 4 ሊካሄድ በታሰበው በዚህ ዝግጅት፤ በመላው እንግሊዝ የሚገኙ የመንግስትና የግል ድርጅቶች፣ የግለሰብ መኖሪያ ቤቶች፣ የንግድ ተቋማትና የተለያዩ ኩባንያዎች በዕለቱ ለአንድ ሰዓት ያህል አምፖሎቻቸውን አጥፍተው ሻማ በመለኮስ የጦርነቱን መጀመር እንዲያስታውሱ አዘጋጆቹ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
እንግሊዝ በጀርመን ላይ ጦርነት ያወጀችበትን ይህን ዕለት በአገሪቱ የሚገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች መብራት በማጥፋት እንደሚዘክሩት ተስፋ አለን ያሉት አዘጋጆቹ፣ ይህ ፕሮጀክት በኪነጥበባዊና ባህላዊ ስራዎች የጦርነትን አስከፊነት የመግለጽ ዓላማ ይዞ መነሳቱን ተናግረዋል፡፡
ጦርነቱ በይፋ በታወጀበት ዕለት ዋዜማ፣ የወቅቱ የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ጸሃፊ ሰር ኤድዋርድ ግሬይ “በመላ አውሮፓ የሚገኙ አምፖሎች ሁሉ ሊጠፉ ነው፤ በህይወት ሳለን ዳግም ተመልሰው ሲበሩ ላናያቸው እንችላለን!” በማለት ለህዝቡ መልዕክታቸውን ማስተላለፋቸውን ያስታወሰው የቢቢሲ ዘገባ፣ ከእሳቸው የዘር ሃረግ የተገኙት አንድሪያን ግሬቭስ የተባሉ ግለሰብ ፕሮጀክቱን በተመለከተ ከትናንት በስቲያ መግለጫ መስጠታቸውን ገልጿል፡፡
አንድሪያን ግሬቭስን ጠቅሶ ቢቢሲ እንዳለው፣ የተለያዩ ዝግጅቶችን ባካተተው በዚህ ፕሮጀክት፣ በአለማቀፍ ደረጃ ታዋቂነትን ያተረፉ አራት የተለያዩ አገራት ዝነኛ አርቲስቶች ጦርነቱን የሚያስታውሱ የስዕል፣ የፊልምና የሙዚቃ ስራዎቻቸውን በስኮትላንድ፣ በዌልስ፣ በሰሜን አየርላንድና በእንግሊዝ በሚገኙ የስነጥበብ ጋለሪዎችና ሲኒማ ቤቶች ለእይታ ያቀርባሉ፡፡የእንግሊዝን ፓርላማ ጨምሮ ታላላቅ የእንግሊዝ ተቋማት በዕለቱ ለአንድ ሰዓት ያህል መብራቶቻቸውን እንደሚያጠፉ የገለጸው ዘገባው፣ ቢቢሲን ጨምሮ ታዋቂ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ደግሞ የስቱዲዮዋቸውን ብርሃን እንደሚያደበዝዙ ይጠበቃል ብሏል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

ባለፈው መጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ 239 ሰዎችን አሳፍሮ ከኳላላምፑር በመነሳት ወደ ቤጂንግ በመብረር ላይ እያለ ድንገት የገባበት የጠፋውን የማሌዢያ አየር መንገድ አውሮፕላን ለማግኘት የተጀመረውና ይህ ነው የሚባል የተጨበጠ ውጤት ያልተገኘበት ፍለጋ አስርት አመታትን ሊፈጅ እንደሚችል የኩባንያው አንድ የስራ ሃላፊ መናገራቸውን ዘ ቴሌግራፍ ዘገበ፡፡
የአየር መንገዱ የንግድ እንቅስቃሴ ዳይሬክተር ሃግ ዳንሌቪ ከሳምንታት በፊት ከኢቭኒንግ ስታንዳርድ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ድንገት በተሰወረው ኤም ኤች 370 ቦይንግ 777 አውሮፕላን ላይ፣ የሆነ የማይገባ ድርጊት ተፈጽሞበታል ብለው እንደሚያስቡና ወደመነሻው ለመመለስ በሚሞክርበት ጊዜም ፈታኝ የሆኑ ነገሮች ተጋርጠውበት ሳይሳካለት እንደቀረ መናገራቸውን ዘገባው አስረድቷል፡፡
አውሮፕላኑ በደቡባዊ የህንድ ውቅያኖስ አካባቢ ሳይወድቅ እንዳልቀረ የገለጹት ዳንሌቪ፣ አወዳደቁ የከፋ ሊሆን እንደሚችልና ውቅያኖሱ ውስጥ ከሚገኙ ተራሮች ጋር ከተጋጨም ስብርባሪው ርቆ ሊሄድና ሊበታተን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
ከዚህ አንጻርም የአውሮፕላኑን ስብርባሪ ለማግኘት የሚደረገው ጥረት እጅግ ፈታኝ ሆኖ ሊቀጥልና ምናልባትም አስርት አመታትን ሊፈጅ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
አውሮፕላኑ ከጠፋ ከቀናት በኋላ፣ ፍለጋውን በተመለከተ ከአንድ የአገሪቱ ከፍተኛ ሚንስትር ጋር ቃለ መጠይቅ እንዳደረገ ያስታወሰው ዘ ቴሌግራፍ፤ ሚንስትሩ በወቅቱ በሰጡት ምላሽ፤ ፍለጋው ሳምንታትን ግፋ ቢልም ወራትን ብቻ ሊፈጅ እንደሚችል ነግረውኝ ነበር ብሏል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

በደራሲ አስፋው ታደሰ የተፃፈው “ዓለም ብላሽ እና ሰባቱ ምስጢራት” የተሰኘ ልቦለድ መፅሀፍ ለንባብ በቃ። መፅሀፉ ስለ እውቀት እና ሞት፣ ስለ ስደትና መንስኤው፣ ስለ ፍቅር፣ ስለ ድህነትና፣ ተፅዕኖው፣ ስለ ኤድስ ታሪካዊ አመጣጥና ሌሎችንም ጉዳዮች ይዳስሳል፡፡ በ98 ገፅ የተቀነበበው መፅሃፉ፤ ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ ለአገር ውስጥ በ25 ብር፣ ለውጭ አገር በ10 ዶላር እየተሸጠ ነው፡፡

በደራሲ ኤሊያስ ማሞ ውባየሁ የተፃፈውና “እንጦሽ” የሚል ርዕስ የተሰጠው ልብወለድ መፅሀፍ ባሳለፍነው ሳምንት በገበያ ላይ ውሏል፡፡ በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥነው መፅሀፍ፤ በውስጡ 38 አጫጭር ልቦለዶችን የያዘ ሲሆን በ240 ገፆች ላይ የተቀነበበ ነው፡፡ “እንጦሽ” ለአገር ውስጥ በ48 ብርና፣ ለውጭ አገር በ18 ዶላር ለሽያጭ ቀርቧል፡፡

ማህበራዊ ወጎችን፣ ትዝብታዊ ጨዋታዎችን፣ እውነተኛ ገጠመኞችንና ሀተታዊ ፅሁፎችን ያካተተው የሄኖክ ግርማ “ኑሮና አዲስ አበባ” የተሰኘ መፅሀፍ ሰሞኑን አንባቢያን እጅ ደርሷል፡፡ መፅሀፉ ከዘሪሁን ህንፃ እስከ ቺቺኒያና አትላስ ያሉ ትዝብቶች፣ ስለሴቶችና ቦርጭ፣ ስለ አረቄ ቤት ጨዋታዎች፣ ስለ ዘመናዊ ልመና (ቅፈላ) እና ሌሎች አዲስ አበባዊ ጉዳዮች ተዳስሰውበታል፡፡ አብዛኛዎቹ ፅሁፎች ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጋዜጦችና መፅሄቶች ተስተናግደው እንደነበርና መጠነኛ ማስተካከያ ተደርጎባቸው በመፅሀፍ መልክ መዘጋጀታቸውንም ደራሲው ገልጿል፡፡ 183 ገፆች ያሉት መፅሀፉ፤ በ40 ብር ከ60 ሳንቲም እየተሸጠ ሲሆን ደራሲው ከዚህ ቀደም “ስልክሽን ልያዘው” እና “ፊት ለፊት ስንኞች” የተሰኘ የግጥም ስብስብ ለንባብ ማብቃቱ ይታወሳል፡፡

በደራሲ ምንባለ ጎሹ የተፃፈውና “ላልተኖረው” የሚል ስያሜ የተሰጠው ልብወለድ መፅሀፍ ሰሞኑን ገበያ ላይ ዋለ፡፡
መቼቱን ጎጃም ፍኖተሰላም እና አካባቢዋ ላይ ያደረገው መፅሀፉ በፍቅርና በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ ሲሆን በ33 ምዕራፎች እና በ243 ገፆች ተመጥኖ ተዘጋጅቷል። መፅሀፉ በ55 ብር ከ70 ሳንቲም እየተሸጠ ነው፡፡

የጐንደር ዩኒቨርስቲን የ60 አመት ጉዞ የሚዘክር “የስልሳ ገፆች ወግ” የተሰኘ መጽሐፍ ታትሞ ለንባብ በቃ፡፡ በጋዜጠኛ አብርሃም ዘሪሁን የተዘጋጀው መጽሐፉ፤ በሁለት ምዕራፎች የተቀናበረ ሲሆን የመጀመሪያው ምዕራፍ ስለ ጐንደር ዩኒቨርስቲ አመሠራረትና ዛሬ የደረሰበትን ደረጃ ሲተነትን ሁለተኛው ምዕራፍ ለዩኒቨርስቲው እድገት አስተዋጽኦ ያበረከቱ ምሁራንን ይዘክራል፡፡
የመጽሐፉ ዋጋ 100 ብር ሲሆን ገቢው ለዩኒቨርስቲው ይውላል ተብሏል፡፡
በሌላ በኩል፤ በአሸናፊ ውዱ የተፃፈው “ሚስት መሆን” የተሰኘ የወግ መጽሐፍ ከትናንት በስቲያ ሀሙስ ምሽት ሰዓት በራስ ሆቴል ተመርቋል፡፡ በ196 ገፆች የተቀነበበው መጽሐፉ፤ በአንድ ሚስቱን በሞት ያጣ ባልና ከሴት ልጁ ጋር አጉል ድርጊት ውስጥ በገባ አባት ታሪክ ላይ የሚያጠነጥን ሲሆን በ50 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡