Saturday, 19 July 2014 11:52

“ምን አደረግኋችሁ!…”

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…ኳሱም አለቀ አይደል! የተናቁት ‘እንትን ያሉበት…’ ኳስ፡፡ እና ‘የተናቀ እንትን ማለቱ…’ በኳስ ብቻ ሳይሆን በሌላም እንዳለ ልብ ይባልልንማ!
የኳስ ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…ሰውየው የእግር ኳስ ዳኛ ነው፡፡ እናላችሁ… በየዓመቱ የልደቱ ቀን በደረሰ ቁጥር ከተለያዩ ቡድኖች ደጋፊዎች በርካታ ‘የልደት’ ካርዶች ይደርሱታል፡፡ ታዲያላችሁ እሱ እንደሚለው፤ የሚደርሱት ካርዶች በሙሉ ሊባል በሚችልበት ሁኔታ አንድ አይነት ምኞት ነበር የሚያስተላልፉት፡፡ “የዘንድሮው የልደት በዓልህ የመጨረሻህ እንዲሆን እመኛለሁ!” አሪፍ አይደል! ልክ ነዋ…‘የሰለጠነ ምኞት’ ማለት ይሄ ነው፡፡
ይሄኔ በሆዳችን ለስንትና ስንት እነ እንትናዎች “….የመጨረሻህ እንዲሆን እመኛለሁ!” ብለን እንደምንመኝ አንድዬ ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡ ክፍት ቦታው ላይ የሚሞላው የግድ ‘ልደት’ ብቻ ላይሆን ይችላል፡፡ ልክ ነዋ…‘ንግግርህ’፣ ‘ዲስኩርህ’፣  ‘ቃለ መጠይቅህ’  ምናምን የሚባሉ በርካታ አማራጮች እንዳሉ ልብ ይባል ብለን ነው፡፡
እግረ መንገዴን… የሆነ ታዋቂ የሆሊዉድ ሰው ነው አሉ፡፡ ታዲያ በብዙ ሰዎች ሥራ ይበሳጫል። እናማ ምን ይላል መሰላችሁ…“አንዳንድ ሰዎች በህይወት የሚቆዩት ሰው መግደል ወንጀል ስለሆነ ብቻ ነው!”
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ሰውየው ንብረቱን ተሸክሞ ሲጓዝ ወንበዴዎች ይገጥሙታል፡፡ እናላችሁ…እስከ ለበሳት ድረስ ሁሉንም ነገር ወስደው መለ መላውን ያስቀሩታል። ከዛላችሁ…ትተውኝ ሄዱ ሲል ጭራሽ በዱላ ያራውጡታል፡፡ ቢቸግረው ምን አለ መሰላችሁ…“ምን አደረግኋችሁ! ንብረቴን ሁሉ ወስዳችሁ፣ አሁን የምትደበድቡኝ አርፍዶ መጣ ብላችሁ ነው!”
አሀ…ምን ያድርግ፡፡ ያለን ሁሉ ተወስዶብን ‘ቆሎ ብንደፋ’ እንኳን ዕዳ መሸፈኛ የሚሆን ‘ሰባራ ሶልዲ’ ሳይኖረንም “ምን አደረግኋችሁ!…” የሚያሰኙ ነገሮች መአት ናቸው፡፡ እኔ የምለው…ሁሌ የምለውን ልድገመውና “ምነው እንዲህ ተከፋፋን!” የምር እኮ ‘የዱር እንትኖች’ እነ አንበሳና አያ ጀቦ መሆናቸው ቀርቶ እኛ ራሳችን የሆንን ሊመስል ምንም አይቀረው፡፡
“በቃ ወድቋል…” ብሎ ትቶ መሄድ የለም። እንደማይነሳም ቢታወቅም እንደገና ‘መሬት እንድትውጠው’ አይነት ይፈለጋል፡፡ ስሙኝማ…በትዳር አካባቢ በተፈጠሩ አለመግባባቶች አንደኛው ወገን ሌላኛውን ለመበቀል የሚሄድበትን ርቀት ስትሰሙ ግርም ይላችኋል፡፡ እናላችሁ፣ ንብረቱን ምኑን ምናምኑን “የእኔ ድርሻ…” “የአንቺ ድርሻ…” ምናምን ተባብለው ከተከፋፈሉ በኋላ የመጽሐፉ ሁለተኛ ክፍል ይቀጥላል፡፡
“እኔን ፈንግላ እሷ ከሌላ ሰው ጋር በሰላም ልትኖር! ሞቻታለኋ!”
“ምን አለች በሉኝ፣ የተወለደበትን ቀን ባላስረግመው!”
ስሙኝማ…የትዳር ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…አንዱ ግራ የገባው ያለውን ስሙኝማ…“ምርጡ ትዳር ማለት የአዳምና የሔዋን ነው፡፡ ምክንያቱም አዳምም ‘ሌሎች ባሎች ለሚስቶቻቻው እንዴት እንደሚንሰፈሰፉላቸው ባየህ፡፡ እኔ እዚህ ዘላለሜን…!’ አይነት ንዝንዝ የለበትም፡፡ እሷም ‘እማዬ እንዴት አይነት ባለሙያ እንደሆነች ባየሻት፡፡ አሁን እንቁላል እንዲህ ነው የሚጠበሰው!...’ አይነት ጭቅጭቅ የለባትም፡፡”
ስሙኝማ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…እውቅ ተዋናይት ናት አሉ፡፡ እናማ…አንድ ግብዣ ላይ የሆነ ይከጅላት የነበረ ሰውን ከብዙ ጊዜ በኋላ ታገኘዋለች፡፡ ታዲያላችሁ ሰውየው አጠገቧ እንደደረሰ አንዳንድ ምክንያታዊ ናቸው ተብለው የሚታሰቡ ‘አካላዊ ለውጦች’ ይታያሉ፡፡ ይሄኔ እሷ ‘ፎቶ ገጭ’ አይነት አስተያየት ታየውና ምን ብትለው ጥሩ ነው… “ኪስህ ውስጥ ሽጉጥ ይዘሀል ወይስ እኔን በማየትህ ደስ ብሎህ ነው…፡፡” እንዴት ሸጋ አባባል ነች!
የምር ግን እኔም እኮ እንትናዬዎች በርከት በሚሉበት አካባቢ…አለ አይደል… “ወንዱ ሁሉ ይሄን ለአተር ማስጫ የሚበቃ  ሞባይል በኪሱ ይዞ የሚዞረው ለምንድነው?” እል ነበር፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
ኑሮን ወደኋላ መለስ ብሎ ላየው አለ ብዙ ነገር ካሁን የሚለየው፣ ድሮማ ቢመለስ እየገሰገሰ ትዝታዉ ተሸሮ ፍቅሩ በነገሰ፡፡
የምትል አሪፍ ስንኝ አለች፡፡ እናማ…የትናንቱ መልካም ነገሮች ሁሉ ትዝታ መሆናቸው ቀርቶ እውን ቢሆኑ የምንል ቁጥራችን እየጨመረ ነው፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ሰዎች አለን የሚሏትን ‘ትዝታ’ መለስ ብለው ቢያዩ የሚገርም አይደለም፡፡ ሰዎች የአሁኑ ራስና ጭራው አልያዝ ሲላቸው፣ የወደፊቱ ድቅድቅ ጨለማ ሲሆንባቸው… አለ አይደል… ‘ቀዌ’ ከመሆን የሚያድናቸው ከትናንት የተራረፈችው መልካም ትዝታ ነች፡፡ ለተወሰነ ደቂቃ “የሰው ክብር የሚታወቅበት፣ አንድ ዳቦ ለአራት ተካፍሎ የሚበላበት፣ ሰው ሲያደናቅፈው “ይድፋህ፣ ሸፋፋ!” ሳይሆን “እኔን ድፍት ያድርገኝ!” ይባልበት የነበረ ዘመን እንደነበረ ማስታወሱ…
ድሮማ ቢመለስ እየገሰገሰ ትዝታዉ ተሽሮ ፍቅሩ በነገሰ ቢያሰኝ አይገርምም፡፡
እናማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል…“ምን አደረግኋችሁ!…” የሚያሰኙ ነገሮች በዝተዋል። በየመሥሪያ ቤቱ ጥርስ የነከሰ አለቃ ምስኪኑን ከሥራ ማስወገድ ወይም ደሞዙን መቆንደድ ብቻ ሳይሆን ሌላም ቦታ ሠርቶ እንዳይበላ ሊያደርገው ነው የሚፈልገው፡፡ የሚጻፍለት ደብዳቤ አንድ ተቀጥሮ ለበርካታ ዓመታት የሠራ ሰው ሳይሆን… አለ አይደል… ጠፍቶ አርጀንቲና ውስጥ ተደብቆ የኖረ የሂትለር የኦሽዊዝ ዘብ ሊያስመስለው ምንም አይቀረው፡
እኔ የምለው…የሆነ ‘ቦስ’ ሰውየውን በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት ከሥራ ካስወጣው በኋላ ሌላ ቦታ ሠርቶ የቤተሰቡን ሆድ እንዳያሸንፍ ማድረግ ምን አይነት ጭካኔ ነው! (እግረ መንገዴን…ይሄን አይነት “አይደለም ተዝናንቶ ምሳ እራት ሊበላ፣ ቆሎ እንዳማረው ድብን ይበላት!” አይነት “ምን አደረግኋችሁ!…” የሚያሰኙ ነገሮች ‘ቦተሊከኞቻችን’ አካባቢ በሽ ነው ይባላል፡፡)
በኪነጥበቡ አካባቢም እንዲህ አይነት ነገሮች ይታያሉ የሚል ወሬ ቢጤ ነገር አለ፡፡ አለ አይደል… የዓይኑ ቀለም ያልተወደደለት፣ ወይም በፈራንካም ሆነ በውሽሜ ‘ጥርስ የገባ’ ምስኪን ጨርቁን ጥሎ እስኪሄድ መከራውን ያያል ይባላል፡፡ በነገራችን ላይ ማበጠሪያ መዋዋስ፣ አንዱ በነካው ብርጭቆ ሌላው መጠጣት ምናምን አይነት ነገሮች እዛ አካባቢ ‘የተለመዱ’ አይደሉም ይባላል፡፡ “ምን አደረግኋችሁ!…” የሚያስብሉ ነገሮች ያስከትላሉ የሚባል ፍርሀት አለ አሉ፡፡
ታዲያ አንቺ ኢትዮዽያ፣ እኛስ ልጆችሽ ምንድነን
አመንኩሽ ማለት የማንችል፣ ፍቅራችን የሚያስነውረን
ዕዳችን የሚያስፎክረን
ግፋችን የሚያስከብረን
ቅንነት የሚያሳፍረን፣ ቂማችን የሚያስደስተን
ኧረ ምንድነን?  ምንድነን?
ብሏል፤ ሎሬት ጸጋዬ በ1957 ዓ.ም.፡፡
እናላችሁ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በኋላም እነኚህ ቃላት ሀያው ናቸው፡፡ ልክ ነዋ…አሁንም በዕዳችን የምንፎክር ነን፡ ከአገር እስከ ግለሰብ ባለዕዳ መሆንን አንገት የሚያስደፋ ሳይሆን የሚያስፎክር ነው፡፡
ግፋችን የሚያስከብረን ሆነናል፡፡ ዘንድሮ የሚከበረው ባለ እውቀቱ ሳይሆን ባለጡንቻው ሆኗል፡፡ በጡንቻ የሚታስብበት ዘመን ውስጥ ነን፡፡ ግፍም የጡንቻ የመጨረሻ ውጤት ነው፡፡ የምንፈልገውን ነገር ለማግኘት ምንም ነገር ከማድረግ ወደኋላ የማንልበት፣ ዓለም የአዋቂዎች ሳይሆን የጉልበተኞች የሆነችበት ዘመን ነው፡፡ እንዲህ ሲሆንም ጊዜ ሚሊዮኖች “ምን አደረግኋችሁ!…” ይላሉ፡፡ ሰሚ የለም እንጂ!
ቅንታችን የሚያሳፍረን ሆነናል፡፡ ቅንነት የሞኝነት መለያ ሆኗል፡፡ ቅንነት ከጊዜ ጋር አብሮ መሄድ አለመቻል ሆኗል፡፡ ቅንነት የጨዋታውን ህግ አለማወቅ ሆኗል፡፡ እንዲህ ሲሆንም ሚሊዮኖች “ምን አደረግኋችሁ!…” ይላሉ፡፡
በቂማችን የምንደሰት ነን፡፡ “የት አባቱ፣ ልክ አገባሁት!” “እኔ ላይ እንዳልዘነጥችብኝ አሁን ብታያት አይደለም ገዥ፣ ሻጭ እንኳን የተጠየፋት ዶሮ አስመስያታለሁ!” አይነት ነገሮች በየዕለት ንግግሮቻችን ውስጥ እየበዙ የሄዱበት ዘመን ነው፡፡ እንዲህ ሲሆንም ሚሊዮኖች “ምን አደረግኋችሁ!…” ይላሉ፡፡ ሰሚ የለም እንጂ!
እናማ…ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት የተጠየቀውን ጥያቄ ደግመን እንጠይቃለን፡፡
ኸረ ምንድነን?  ምንድነን?
“ምን አደረግኋችሁ!…” ከሚያስብሉ ነገሮች ይሰውረንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Published in ባህል
Saturday, 19 July 2014 11:52

“ምን አደረግኋችሁ!…”

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…ኳሱም አለቀ አይደል! የተናቁት ‘እንትን ያሉበት…’ ኳስ፡፡ እና ‘የተናቀ እንትን ማለቱ…’ በኳስ ብቻ ሳይሆን በሌላም እንዳለ ልብ ይባልልንማ!
የኳስ ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…ሰውየው የእግር ኳስ ዳኛ ነው፡፡ እናላችሁ… በየዓመቱ የልደቱ ቀን በደረሰ ቁጥር ከተለያዩ ቡድኖች ደጋፊዎች በርካታ ‘የልደት’ ካርዶች ይደርሱታል፡፡ ታዲያላችሁ እሱ እንደሚለው፤ የሚደርሱት ካርዶች በሙሉ ሊባል በሚችልበት ሁኔታ አንድ አይነት ምኞት ነበር የሚያስተላልፉት፡፡ “የዘንድሮው የልደት በዓልህ የመጨረሻህ እንዲሆን እመኛለሁ!” አሪፍ አይደል! ልክ ነዋ…‘የሰለጠነ ምኞት’ ማለት ይሄ ነው፡፡
ይሄኔ በሆዳችን ለስንትና ስንት እነ እንትናዎች “….የመጨረሻህ እንዲሆን እመኛለሁ!” ብለን እንደምንመኝ አንድዬ ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡ ክፍት ቦታው ላይ የሚሞላው የግድ ‘ልደት’ ብቻ ላይሆን ይችላል፡፡ ልክ ነዋ…‘ንግግርህ’፣ ‘ዲስኩርህ’፣  ‘ቃለ መጠይቅህ’  ምናምን የሚባሉ በርካታ አማራጮች እንዳሉ ልብ ይባል ብለን ነው፡፡
እግረ መንገዴን… የሆነ ታዋቂ የሆሊዉድ ሰው ነው አሉ፡፡ ታዲያ በብዙ ሰዎች ሥራ ይበሳጫል። እናማ ምን ይላል መሰላችሁ…“አንዳንድ ሰዎች በህይወት የሚቆዩት ሰው መግደል ወንጀል ስለሆነ ብቻ ነው!”
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ሰውየው ንብረቱን ተሸክሞ ሲጓዝ ወንበዴዎች ይገጥሙታል፡፡ እናላችሁ…እስከ ለበሳት ድረስ ሁሉንም ነገር ወስደው መለ መላውን ያስቀሩታል። ከዛላችሁ…ትተውኝ ሄዱ ሲል ጭራሽ በዱላ ያራውጡታል፡፡ ቢቸግረው ምን አለ መሰላችሁ…“ምን አደረግኋችሁ! ንብረቴን ሁሉ ወስዳችሁ፣ አሁን የምትደበድቡኝ አርፍዶ መጣ ብላችሁ ነው!”
አሀ…ምን ያድርግ፡፡ ያለን ሁሉ ተወስዶብን ‘ቆሎ ብንደፋ’ እንኳን ዕዳ መሸፈኛ የሚሆን ‘ሰባራ ሶልዲ’ ሳይኖረንም “ምን አደረግኋችሁ!…” የሚያሰኙ ነገሮች መአት ናቸው፡፡ እኔ የምለው…ሁሌ የምለውን ልድገመውና “ምነው እንዲህ ተከፋፋን!” የምር እኮ ‘የዱር እንትኖች’ እነ አንበሳና አያ ጀቦ መሆናቸው ቀርቶ እኛ ራሳችን የሆንን ሊመስል ምንም አይቀረው፡፡
“በቃ ወድቋል…” ብሎ ትቶ መሄድ የለም። እንደማይነሳም ቢታወቅም እንደገና ‘መሬት እንድትውጠው’ አይነት ይፈለጋል፡፡ ስሙኝማ…በትዳር አካባቢ በተፈጠሩ አለመግባባቶች አንደኛው ወገን ሌላኛውን ለመበቀል የሚሄድበትን ርቀት ስትሰሙ ግርም ይላችኋል፡፡ እናላችሁ፣ ንብረቱን ምኑን ምናምኑን “የእኔ ድርሻ…” “የአንቺ ድርሻ…” ምናምን ተባብለው ከተከፋፈሉ በኋላ የመጽሐፉ ሁለተኛ ክፍል ይቀጥላል፡፡
“እኔን ፈንግላ እሷ ከሌላ ሰው ጋር በሰላም ልትኖር! ሞቻታለኋ!”
“ምን አለች በሉኝ፣ የተወለደበትን ቀን ባላስረግመው!”
ስሙኝማ…የትዳር ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…አንዱ ግራ የገባው ያለውን ስሙኝማ…“ምርጡ ትዳር ማለት የአዳምና የሔዋን ነው፡፡ ምክንያቱም አዳምም ‘ሌሎች ባሎች ለሚስቶቻቻው እንዴት እንደሚንሰፈሰፉላቸው ባየህ፡፡ እኔ እዚህ ዘላለሜን…!’ አይነት ንዝንዝ የለበትም፡፡ እሷም ‘እማዬ እንዴት አይነት ባለሙያ እንደሆነች ባየሻት፡፡ አሁን እንቁላል እንዲህ ነው የሚጠበሰው!...’ አይነት ጭቅጭቅ የለባትም፡፡”
ስሙኝማ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…እውቅ ተዋናይት ናት አሉ፡፡ እናማ…አንድ ግብዣ ላይ የሆነ ይከጅላት የነበረ ሰውን ከብዙ ጊዜ በኋላ ታገኘዋለች፡፡ ታዲያላችሁ ሰውየው አጠገቧ እንደደረሰ አንዳንድ ምክንያታዊ ናቸው ተብለው የሚታሰቡ ‘አካላዊ ለውጦች’ ይታያሉ፡፡ ይሄኔ እሷ ‘ፎቶ ገጭ’ አይነት አስተያየት ታየውና ምን ብትለው ጥሩ ነው… “ኪስህ ውስጥ ሽጉጥ ይዘሀል ወይስ እኔን በማየትህ ደስ ብሎህ ነው…፡፡” እንዴት ሸጋ አባባል ነች!
የምር ግን እኔም እኮ እንትናዬዎች በርከት በሚሉበት አካባቢ…አለ አይደል… “ወንዱ ሁሉ ይሄን ለአተር ማስጫ የሚበቃ  ሞባይል በኪሱ ይዞ የሚዞረው ለምንድነው?” እል ነበር፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
ኑሮን ወደኋላ መለስ ብሎ ላየው አለ ብዙ ነገር ካሁን የሚለየው፣ ድሮማ ቢመለስ እየገሰገሰ ትዝታዉ ተሸሮ ፍቅሩ በነገሰ፡፡
የምትል አሪፍ ስንኝ አለች፡፡ እናማ…የትናንቱ መልካም ነገሮች ሁሉ ትዝታ መሆናቸው ቀርቶ እውን ቢሆኑ የምንል ቁጥራችን እየጨመረ ነው፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ሰዎች አለን የሚሏትን ‘ትዝታ’ መለስ ብለው ቢያዩ የሚገርም አይደለም፡፡ ሰዎች የአሁኑ ራስና ጭራው አልያዝ ሲላቸው፣ የወደፊቱ ድቅድቅ ጨለማ ሲሆንባቸው… አለ አይደል… ‘ቀዌ’ ከመሆን የሚያድናቸው ከትናንት የተራረፈችው መልካም ትዝታ ነች፡፡ ለተወሰነ ደቂቃ “የሰው ክብር የሚታወቅበት፣ አንድ ዳቦ ለአራት ተካፍሎ የሚበላበት፣ ሰው ሲያደናቅፈው “ይድፋህ፣ ሸፋፋ!” ሳይሆን “እኔን ድፍት ያድርገኝ!” ይባልበት የነበረ ዘመን እንደነበረ ማስታወሱ…
ድሮማ ቢመለስ እየገሰገሰ ትዝታዉ ተሽሮ ፍቅሩ በነገሰ ቢያሰኝ አይገርምም፡፡
እናማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል…“ምን አደረግኋችሁ!…” የሚያሰኙ ነገሮች በዝተዋል። በየመሥሪያ ቤቱ ጥርስ የነከሰ አለቃ ምስኪኑን ከሥራ ማስወገድ ወይም ደሞዙን መቆንደድ ብቻ ሳይሆን ሌላም ቦታ ሠርቶ እንዳይበላ ሊያደርገው ነው የሚፈልገው፡፡ የሚጻፍለት ደብዳቤ አንድ ተቀጥሮ ለበርካታ ዓመታት የሠራ ሰው ሳይሆን… አለ አይደል… ጠፍቶ አርጀንቲና ውስጥ ተደብቆ የኖረ የሂትለር የኦሽዊዝ ዘብ ሊያስመስለው ምንም አይቀረው፡
እኔ የምለው…የሆነ ‘ቦስ’ ሰውየውን በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት ከሥራ ካስወጣው በኋላ ሌላ ቦታ ሠርቶ የቤተሰቡን ሆድ እንዳያሸንፍ ማድረግ ምን አይነት ጭካኔ ነው! (እግረ መንገዴን…ይሄን አይነት “አይደለም ተዝናንቶ ምሳ እራት ሊበላ፣ ቆሎ እንዳማረው ድብን ይበላት!” አይነት “ምን አደረግኋችሁ!…” የሚያሰኙ ነገሮች ‘ቦተሊከኞቻችን’ አካባቢ በሽ ነው ይባላል፡፡)
በኪነጥበቡ አካባቢም እንዲህ አይነት ነገሮች ይታያሉ የሚል ወሬ ቢጤ ነገር አለ፡፡ አለ አይደል… የዓይኑ ቀለም ያልተወደደለት፣ ወይም በፈራንካም ሆነ በውሽሜ ‘ጥርስ የገባ’ ምስኪን ጨርቁን ጥሎ እስኪሄድ መከራውን ያያል ይባላል፡፡ በነገራችን ላይ ማበጠሪያ መዋዋስ፣ አንዱ በነካው ብርጭቆ ሌላው መጠጣት ምናምን አይነት ነገሮች እዛ አካባቢ ‘የተለመዱ’ አይደሉም ይባላል፡፡ “ምን አደረግኋችሁ!…” የሚያስብሉ ነገሮች ያስከትላሉ የሚባል ፍርሀት አለ አሉ፡፡
ታዲያ አንቺ ኢትዮዽያ፣ እኛስ ልጆችሽ ምንድነን
አመንኩሽ ማለት የማንችል፣ ፍቅራችን የሚያስነውረን
ዕዳችን የሚያስፎክረን
ግፋችን የሚያስከብረን
ቅንነት የሚያሳፍረን፣ ቂማችን የሚያስደስተን
ኧረ ምንድነን?  ምንድነን?
ብሏል፤ ሎሬት ጸጋዬ በ1957 ዓ.ም.፡፡
እናላችሁ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በኋላም እነኚህ ቃላት ሀያው ናቸው፡፡ ልክ ነዋ…አሁንም በዕዳችን የምንፎክር ነን፡ ከአገር እስከ ግለሰብ ባለዕዳ መሆንን አንገት የሚያስደፋ ሳይሆን የሚያስፎክር ነው፡፡
ግፋችን የሚያስከብረን ሆነናል፡፡ ዘንድሮ የሚከበረው ባለ እውቀቱ ሳይሆን ባለጡንቻው ሆኗል፡፡ በጡንቻ የሚታስብበት ዘመን ውስጥ ነን፡፡ ግፍም የጡንቻ የመጨረሻ ውጤት ነው፡፡ የምንፈልገውን ነገር ለማግኘት ምንም ነገር ከማድረግ ወደኋላ የማንልበት፣ ዓለም የአዋቂዎች ሳይሆን የጉልበተኞች የሆነችበት ዘመን ነው፡፡ እንዲህ ሲሆንም ጊዜ ሚሊዮኖች “ምን አደረግኋችሁ!…” ይላሉ፡፡ ሰሚ የለም እንጂ!
ቅንታችን የሚያሳፍረን ሆነናል፡፡ ቅንነት የሞኝነት መለያ ሆኗል፡፡ ቅንነት ከጊዜ ጋር አብሮ መሄድ አለመቻል ሆኗል፡፡ ቅንነት የጨዋታውን ህግ አለማወቅ ሆኗል፡፡ እንዲህ ሲሆንም ሚሊዮኖች “ምን አደረግኋችሁ!…” ይላሉ፡፡
በቂማችን የምንደሰት ነን፡፡ “የት አባቱ፣ ልክ አገባሁት!” “እኔ ላይ እንዳልዘነጥችብኝ አሁን ብታያት አይደለም ገዥ፣ ሻጭ እንኳን የተጠየፋት ዶሮ አስመስያታለሁ!” አይነት ነገሮች በየዕለት ንግግሮቻችን ውስጥ እየበዙ የሄዱበት ዘመን ነው፡፡ እንዲህ ሲሆንም ሚሊዮኖች “ምን አደረግኋችሁ!…” ይላሉ፡፡ ሰሚ የለም እንጂ!
እናማ…ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት የተጠየቀውን ጥያቄ ደግመን እንጠይቃለን፡፡
ኸረ ምንድነን?  ምንድነን?
“ምን አደረግኋችሁ!…” ከሚያስብሉ ነገሮች ይሰውረንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Published in ባህል

     ዛሬ የማስታውሰውን ያህል መስፍን ስለነገረኝ ነገር ልንገራችሁ፡፡ መስፍን ሀብተማርያም፤ ስለእሱና ስለጥላሁን ገሠሠ የፍቅር ልምድ፤ አንድ ቀን ሲያጫውተኝ፣ እንዲህ አለኝ፡፡ (መቼም አፉ እንዴት እንደሚጣፍጥ አይነገርም!)
“ድሮ ነው፡፡ አንዴ፤ አንዲት አዲስ ውስኪ ቤት የከፈተች ቆንጆ ሴትዮ ቤት ገብቼ ሳጫውታት፣ አምራኝ፣ ወዳኝ፣ ተሟሙቀን፣ ለፍቅር አንድ ሀሙስ ቀርቶናል፡፡ የማውቃቸውን አጫጭር ልብወለዶች ከነሐሚንግዌይ፣ ከነአላንፓ፣ ከነኦሄንሬ እየጨለፍኩ እያጣፈጥኩ እየነገርኳት፤ ልቧን አሳስቼዋለሁ.. ዐይኗ ይንከራተታል… ቆንጆ አቋመ - ውበቴ ላይ መላ ሰውነቷ በፍፁም ፈቃዷ ተደርቧል፡፡ አፏ ጆሮ የሆነ ያህል ተከፍቶ ያዳምጠኛል፡፡… በማህል ሲያቀብጠኝ ጥላሁን ገሠሠጋ ደወልኩ፡፡ (እንዲች ዓይነት ቆንጆ ማርኬያለሁ ብዬ ጉራዬን ልነዛበት ነው፡፡) ጥላሁን “የት አካባቢ ነው?” አለኝ፡፡ “ፓስተር አካባቢ” አልኩት፡፡ ከአንድ ከሃያ ደቂቃ በኋላ ከች አለ! ከዚያ መጣና አያት፡፡ ስገምት፣ የጦር መሳሪያ መርጧል “የህይወቴ ህይወትን” ጣዕመ - ዜማ!! አንድ ሁለት ደብል በኔው ሂሳብ ገጨና “የህይወቴ ህይወት አንቺ በመሆንሽ…” ማለት ጀመረ፡፡ ዘፈነ፡፡ መድረክ ላይ እንዲዚህ ሲዘፍን ሰምቼው አላውቅም!... አለቀ፡፡
እኔና ልጅቷ ተለያየን፡፡ ከጥላሁን ጋር የሆኑትን ሆኑ!” አለኝ መስፍን፡፡ የሚከተለው ግጥም የዚያ ስሜት ነው፡፡


======================

 


ፈጠራ እንደምችል ገብቶኛለ ያን ለታ!
ነ.መ

ስትነግረኝ --- ስትነግረኝ
ጥበብክን፣ ስትነግረኝ
“ተው ይረክሳል!” ስልህ
“ተወኝ ላውራ” ብለህ
ልታወራኝ መርጠህ
“ስማኝ ብቻ!” ብለህ …
ረከሰም ባልል፣ ምን ትተህልኝ ሄድህ
አንተን አላተረፍኩ፤ አልተረፈኝ ቃልህ፡፡
ትዝ ያለኝን ላትት፣ መኖር ጣሩ እሱ ነው
መግጠም ፍሬ ማፍራት፣ ሌላ ምን ፀጋ አለው?
በግጥም ላስቀምጠው፣ እንዲህ ነበር ያልከኝ:-
“ከድርሰት አብነት፣ ከፈጠራ ሥራ
ከሥነ-ፅሁፍ ወግ፣ ከሄኒንግዌ’ ሤራ
ከውበት አማልክት፣ የጥበባት ጎራ
ሳወራ ሳወራ፤
ጥላሁን ገሠሠ፣ በልጦ ከኔ ትምርት
በ“ህይወቴ ህይወት”፣ ቆንጆዬን ወሰዳት!”
ያልከኝን አልረሳም፡፡
ቃል ይሻል፣ ድምፅ ይሻል፣ አልገባኝም ዛሬም፡፡
መጻህፍት አብበው፣ ቢደምቁ ቢሰሙ
አጭር ልቦለዶች፣ ቢፈኩ ቢተሙ
እንዳንተም ያለ ሰው፣ በልባም ከንፈሮች
በለዛ መዐዛ፣ በወዙ ሐረጐች
ሺ ተረት ቢተርት፣ ሺ ቃላት ቢሞሽር
ያቺን ቆንጆ ሎጋ፣ ምን ምኗን ቢወድር
ያችን ውብ አለንጋ፣ ምን ገላዋን ቢያሾር
አፏን አከላቷን፣ ከፍታ ብታዳምጥ
ብታቅፍ፣ ብታግል፣ ሁሏን ብታተኩስ
ራሷም ብትነድ፣ ከላይ እታች ድረስ
… ዘፋኙ ሲመጣ፣ እንዲህ ሁሉም ሲሻር
ለካ ፍቅር የለም፣ ድምፅ ሳይጨመር
ያልከኝን አልረሳም…
ብዕሬን ሰበሰብኩ፣ ጥላሁን ሲመጣ
ለካ-ሥነ-ፅሁፍ፣ ቅላፄ ሳይሰንቅ፣ ዳገትም አይወጣ!
ድምፅ ሲስረቀረቅ፣ ቆንጆ አቅሏን ስታጣ
ተፈጥሮን አየሁት፣ ትምህርትን ሲቀጣ!
ያልከኝን አልረሳም…
ወዳጅህ ነው ጥሌ
ወዳጁ ነህ አንተም
ግን በዜማ ዝናብ፣ ያኔ መሸነፍክን
በመለኮት ቃና፣ ቆንጆ መነጠክን
አምነህ ነግረኸኛል፣ በኪነ-ጥበብ ሥን
ሰማይና መሬት፣ ያን ያህል መራቁን!!
ባማለልካት ቆንጆ፣ ባሞቅኸው ገበታ
ጥላሁን ሲከሰት፣ ባስረከብከው ቦታ
አንት ያበሰልከውን
የላቀህ መብላቱን
በነገርከኝ አፍታ፤
መስፍኔ ልንገርህ …
ፈጠራ እንደምትችል፣ ገብቶኛል ያን ለታ!
ፍፁም ደግነት ነው፣ በሚችል መበለጥ
ዘመንን ይልቃል፣ ዕውነትን የሚመርጥ!
ሐምሌ 10/2006 ዓ.ም
(ለመስፍን ሀብተማርያም እና ለጥላሁን ገሠሠ)

Published in ባህል


በመጪው ምርጫ የኢህአዴግ ደጋፊ የሆነ ”ተቃዋሚ ፓርቲ” ያስፈልገናል
ዶ/ር አሸብር ኢህአዴግን በድጋሚ ማሸነፍ አይፈልጉም!
ኢቴቪን የተመለከተ ዶክመንተሪ የሚሰራ አገር ወዳድ እንዴት ጠፋ?


ባለፈው ቅዳሜ በዚሁ ጋዜጣ ላይ የቀረበው የዶ/ር አሸብር ቃለ ምልልስ በእጅጉ አዝናንቶኛል፡፡ (ቃለ ምልልስ ነው ወይስ ማመልከቻ?) ባይገርማችሁ… በቃለ ምልልሱ ላይ የተናገሩት በአብዛኛው ለህዝቡ ሳይሆን  ለኢህአዴግ ፅ/ቤት ነው የሚመስለው፡፡ (እኛ ገዢ ፓርቲ አይደለንማ!)  እኚህ ሰው የዛሬ 4 ዓመት ለምርጫ ሲወዳደሩም ዘና እንዳደረጉን ትዝ ይለኛል - “የኢህአዴግ ደጋፊ፤ የግል ተወዳዳሪ ነኝ” በማለት፡፡ የኢህአዴግ ደጋፊ ነኝ ቢሉም ኢህአዴግ ያቀረበውን እጩ ተፎካካሪ አሸንፈው ፓርላማ የገቡ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፖለቲከኛ ሳይሆኑ አይቀሩም፡፡
ዶ/ር አሸብር በ2002 ምርጫ ከኢህአዴግ ጋር ተወዳድረው ማሸነፋቸውን ግን  የወደዱት አይመስለኝም። እኔ ከቃለ-ምልልሳቸው የተረዳሁት መፀፀታቸውን ነው፡፡ በምርጫው የተወዳደሩት አንድ የኢህአዴግ አባል የሆኑ ግለሰብ በፈፀሙባቸው በደል እንደሆነ ያስታወሱት ዶ/ሩ፤ ፈፅሞ ኢህአዴግን ተቃውመው አለመወዳደራቸውን አስረግጠው ተናገረዋል፡፡ (ኢህአዴግ እጩውን ቀይሮ ቢሆን ኖሮ አልወዳደርም ነበር ብለዋል!) እኔ የምለው… ሰው ለምርጫ የሚወዳደረው ህዝብ ለማገልገል ነው ወይስ በደል ለመቀበል?  (ለሁለቱም ይቻላል እንዳትሉኝ!)
በመጪው ምርጫ ለመወዳደር ገና ባይወስኑም ድንገት በምርጫው ቢሳተፉ እንኳ ኢህአዴግን በድጋሚ ባይወዳደሩት ደስ እንደሚላቸው ተናግረዋል (በድጋሚ እንዳያሸንፉት ፈርተው እኮ ነው!) ከንግግራቸው ትንሽ ግራ ያጋባኝ ግን  ምን መሰላችሁ? ኢህአዴግ መዝኖ ፈተናውን አልፈሃል ወይም ወድቀሃል ይበለኝ-- ያሉት ነገር ነው፡፡ ኢህአዴግ እኮ የራሱን አባል እንጂ የግል ተወዳዳሪ ገምግሞ አያውቅም፡፡ (በክፍያ የግምገማ አገልግሎት መስጠት ጀምሮ ይሆን እንዴ?)
የዶክተር አሸብር ቃለምልልስ የሚያዝናና ብቻ ሳይሆን የሚያስገርምም ነው፡፡ በፓርላማው የተቃዋሚዎች አለመኖር ብዙም የሚያሳስባቸው አይመስሉም - ከቃለ ምልልሱ እንደተረዳሁት፡፡ እንደሳቸው ዓይነት “የኢህአዴግ ደጋፊ የግል ተወዳዳሪ” ካሉ በቂ ነው ብለው የደመደሙ ይመስላል፡፡ ለዚህ ነው ፓርላማው ውስጥ 100 ፐርሰንት አንድ ፓርቲ ቢሆን ነውር የለውም ያሉት፡፡ (እንኳንም የግል ተወዳዳሪ ሆኑልን!) ገዢው ፓርቲ ቢሆኑ እኮ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ያከትምለት ነበር፡፡ በግል ክሊኒክ ባለቤትነት የሚታወቁት ዶ/ር አሸብር  ነጋዴዎች ከባንክ ብድር ማግኘት አልቻልንም ማለታቸውን በተመለከተ የሰጡት አስተያየትም አግራሞት የሚፈጥር ነው፡፡ እንደውም የሚበደር ነው የጠፋው ብለዋል፡፡ ምናልባት በቅርቡ ስብሰባ ተካፍለው ከመጡበት አገር ጋር ተምታቶባቸው ይሆን እንዴ? (“ጋዜጠኛዋ ስለኢትዮጵያ እኮ ነው የምጠይቅዎት!” ብላ በድጋሚ ጥያቄዋን ማንሳት ነበረባት!)
በተረፈ ግን እሳቸው “የኢህአዴግ ደጋፊ የግል ተወዳዳሪ” እንደሚሉት ሁሉ፣ ለ2007 ምርጫ  የኢህአዴግ ደጋፊ ተቃዋሚ ፓርቲ ማቋቋም ያስፈልገናል ብዬ አስባለሁ፡፡ ለምን መሰላችሁ - ትንሽ ዘና እንድንል ያደርገናል፡፡ እንኳን በፓርቲ ደረጃ የግል ተወዳዳሪ እንኳን እንዴት እንደሚያዝናና አይታችሁት የለ! ምርጫ ቦርድ ለእንዲህ ያለ ፓርቲ ፈቃድ ይሰጥ ይሆን? (አጣሩልኛ!)     
አሁን ደግሞ ወደ ሌላ አጀንዳ እንለፍ፡፡ መንግስት “ዲሞክራሲ የምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው” እያለ በተደጋጋሚ ሲናገር እየሰማነው ነው፡፡ በተግባር ግን ገና አላስመሰከረም ይላሉ - አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች፡፡ እውነታቸውን ይሆን? (በመረጃ ላይ ተደግፎ መወቃቀስ የሥልጣኔ ምልክት ነው!)
ኢህአዴግ ከጥቂት ዓመታት በፊት ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ የመፍጠር ህልም እንዳለው በይፋ ሲናገር “ዓይንህን ላፈር” የሚሉት ወገኖች ሳይቀሩ “ዋው!” ብለው ነበር - በአድናቆት!! (ማድነቅ ሲያንሳቸው ነው!) ገዢ ፓርቲ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓትን ለማጎልበት እንዲህ ያለ ቁርጠኝነት ሲያሳይ እንኳንስ በጦቢያ በአፍሪካም የመጀመሪያው ሳይሆን አይቀርም፡፡
በ2002 አገራዊ ምርጫ ኢህአዴግ በ98 ነጥብ ምናምን (ከመቶ ማለት ነው!) ድምፅ ምርጫውን ማሸነፉን ተከትሎ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ በመስቀል አደባባይ ለታደመው የኢህአዴግ ደጋፊና ለተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ባደረጉት ንግግር “ያሸነፈው ይሄኛው ወይም ያኛው ፓርቲ ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ ነው” ማለታቸው ይታወሳል (የማንዴላን ንግግር እኮ ነው የሚመስለው!) ይሄን ጊዜ ታዲያ ብዙዎች “ኢህአዴግ ልብ ገዛ” ብለው ነበር፡፡ (አይጠቀምበትም እንጂ ራሱ አለው እኮ!)
ጠ/ሚኒስትሩ፤በዚያው ሰሞን ለኢቴቪ በሰጡት ቃለ ምልልስ፤ ምንም እንኳን ተቃዋሚዎች በፓርላማ ውክልና ባያገኙም መንግስታቸው በአገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚሳተፉበትን መንገድ እንደሚያመቻች ተናግረው ነበር። ይሄኔ ነው ኢህአዴግ በአንድ ዓመት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ “ዋው!” የሚል አድናቆት የተቸረው፡፡ (አሁን ግን  ሁለቱም  አድናቆቶች በእጁ ላይ የሉም!)
ኢህአዴግ ክፉ ሆኖ ሳይሆን እንደዕድል ሆኖበት ሁለቱንም የተናገራቸውን ነገሮች ሳያሳካ ቀርቷል፡፡ ሲመኝ የኖረውን  ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ አልፈጠረም። ፓርላማ ያልገቡ ተቃዋሚዎች በአገር ጉዳይ ላይ የመምከር ዕድል ያገኛሉ ያለውም አልተሳካለትም፡፡ ሁለት አልሞ ሁለቱንም ስቷል! (አልሞ መተኮስን ረስቷል ልበል?)  በነገራችሁ  ላይ በአገሪቱ ውስጥ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ አለመፈጠሩ ከማንም በላይ እኔን ነው የጎዳኝ ሲል ተናዝዟል - ኢህአዴግ፡፡ የተቃዋሚዎችን ሚና ራሱ እንዲወጣ መገደዱን በመግለፅ፡፡  (አንዴ ገዢ ፓርቲ፣ አንዴ ተቃዋሚ እየሆኑ መተወን  ፈታኝ ነው!) ትራጄዲው ደግሞ ምን መሰላችሁ? ኢህአዴግ የተመኘውን ጠንካራ ተቃዋሚ የመፍጠር ህልሙን አለማሳካቱ ሳያንሰው በፓርላማ የተፈረጁ የተቃዋሚ ድርጅቶችን ማፍራቱ ነው፡፡ (ወደድንም ጠላንም የእኛው እዳዎች ናቸው!)
እኔ የምለው … በወዲያኛው ሳምንት ኢቴቪ በግል ፕሬሱ አጀማመርና ሂደት ላይ ያቀረበውን ዶክመንተሪ እንዴት አያችሁት? ለኔ መቼም ከሌላው ጊዜ በእጅጉ የተሻለ ነበር፡፡ የአቅሙን ያህል ሚዛናዊ ለመሆን ሞክሯል። ሙሉ በሙሉ ሚዛናዊ ነው እንዳንለው ግን ቢያንስ  ስም ሳይጠቀስ በምስል እየታዩ ሲወነጀሉ የነበሩትን የፕሬስ ውጤቶች ሃሳብ አላካተተም፡፡ በነገራችሁ ላይ አንድ የኢህአዴግ ኃላፊ የግል ፕሬስ ዓላማ ምን መሆን እንዳለበት ሲያስረዱ፤ “የግል ፕሬስ ፈቃድ ማውጣት ያለበት ኢህአዴግን ለመጣል  ሳይሆን የዛሬ 50 እና 100 ዓመት እነ “ዎል ስትሪት” የደረሱበት ደረጃ ላይ ለመድረስ አልሞ መሆን አለበት“ ብለዋል - በዶክመንተሪው ላይ፡፡ (እነ “ዎል ስትሪት” የኒዮሊበራል አቀንቃኞች አይደሉም እንዴ?)
በነገራችሁ ላይ ኢቴቪ በግሉ ፕሬስ፣ በቀለም አብዮት፣ በተቃዋሚዎች፣ በአሸባሪዎችና በአክራሪዎች ዙሪያ ዶክመንተሪዎች እየሰራ ለማቅረብ እንዴት መከራውን እንደበላ እማኞቹ እኛ ነን፡፡ (እንደ ኢቴቪ  የልማታዊ ጋዜጠኝነት ሚናውን የተወጣ የለም!) ግን ምን ያደርጋል? የሰራን የማድነቅና የማበረታታት ባህል የለንም፡፡ እናም አንዴም ሳይሸለምና ሳይደነቅ ወደ ኮርፖሬሽንነት ሊለወጥ ነው፡፡ እሺ ሽልማቱም ይቅር .. እንዴት አንድ እንኳን ዶክመንተሪ የሚሰራለት ያጣል? የአገር ዶክመንተሪ እየሰራ ህፀፅ የሚነቅስ ተቋም፣የእሱን ዶክመንተሪ ሰርቶ ህፀፁን የሚነቅስለት እንዴት ያጣል ?(“የአባይን ልጅ ውሃ ጠማው” ማለት ይሄኔ ነው!)
ኢቴቪ በግል ፕሬሱ ዙሪያ ያሰናዳውን ዶክመንተሪ ባቀረበልን ማግስት (መቼም ግጥምጥሞሽ መሆን አለበት!) ከሰባት አስርት ዓመታት ዕድሜ በላይ ያስቆጠረው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት “የወረቀት ዋጋ እጅግ ንሯል” በማለት፣ የህትመት ዋጋ ላይ ከ25-35 በመቶ ጭማሪ ማድረጉ ተነግሯል፡፡ ይሄም የግል ፕሬሱን ህልውና ስጋት ላይ እንደጣለ አሳታሚዎች በምሬት ተናግረዋል፡፡ ልብ በሉ! የዋጋ ጭማሪው የ5 ወይም የ10 በመቶ አይደለም፡፡ እርግጠኛ ነኝ ማተሚያ ቤቱ የግል ቢሆን ኖሮ ሌሎች አማራጮችን ይወስዳል እንጂ ይሄን ሁሉ ጭማሪ በአንድ ጊዜ ደንበኞቹ ላይ አይጭንም፡፡ ብርሃንና ሰላም ግን ይሄ ሁሉ ደንታ አልሰጠውም (“ልማታዊ የመንግስት ተቋም” ነዋ!)
በነገራችሁ ላይ እንኳን ዋጋ ሲጨምር ቀርቶ የእሁድ ጋዜጣን ማክሰኞ፣ የቅዳሜውን እሁድ ሲያወጣም እኮ ደንታ ሰጥቶት አያውቅም፡፡ (ለምን ብሎ ይጨነቃል?) ብርሃንና ሰላም እኮ እንደእነ ቴሌና መብራት ኃይል  ነው፡፡(ደንበኞቹ አማራጭ እንደሌላቸው አሳምሮ ያውቃል!) እውነቱን ልንገራችሁ አይደል --- ጨክነን ከቻይና ማተሚያ ቤቶች ጋር ብንቀራረብ እኮ ከብርሃንና ሰላም የተሻለ ፈጣን አገልግሎት እናገኛለን፡፡ ተርብ የሆኑ የቻይና የህትመት ባለሙያዎች አስር የማይሞሉ  የኢትዮጵያ ሳምንታዊ ጋዜጦችን  በእለቱ ማውጣት አያቅታቸውም! (ቢዝነስና ፖለቲካን አይቀላቅሉማ!)   
መነሻዬ ላይ ኢህአዴግ “ለአገሪቱ ዲሞክራሲ የምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው” እያለ መወትወቱን ያነሳሁት ለዋዛ ፈዛዛ አይደለም፡፡ ለቁምነገር ነው፡፡ አያችሁ… የዲሞክራሲ ነገር ከልቡ የሚያሳስበው ከሆነ የህትመት ዋጋ ጭማሪውን እንደሌላው ጊዜ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ሊያልፈው አይችልም፡፡ የግል ፕሬሱ ከጨዋታ ውጭ ሆነ ማለት የዲሞክራሲ ሥርአቱን እንዴት ከስሩ እንደሚነቀንቀው መገመት አያቅተውም፡፡ የቱንም ያህል የግሉ ፕሬስ ባይመቸውም ለዲሞክራሲው መጎልበት ሲል አንድ ነገር ማድረጉ አይቀርም፡፡ (ማመልከቻ መሰለብኝ እንዴ? ነው እኮ!)
ይኸውላችሁ--- ወደ አገር ውስጥ የሚገባ የህትመት ወረቀት ላይ የተጣለውን ቀረጥ በማንሳት ብቻ መንግስት ለዲሞክራሲው መጎልበት ያለውን ቁርጠኝነት ማሳየት ይችላል፡፡ (“ለዲሞክራሲ ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ”--እንዲሉ) ያለዚያ እኮ የኢትዮጵያ የግል ፕሬስ ኢህአዴግ በስልጣን ላይ የቆየበትን ዕድሜ ያህል ሳያስቆጥር እንኳ ሊያከትም ነው ማለት ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የዶ/ር አሸብር አስተያየት ምን እንደሆነ ባውቅ ደስ ይለኝ ነበር፡፡ (ዘና ለማለት እኮ ነው!) 

Saturday, 19 July 2014 11:45

የፖለቲካ ጥግ

የሥራ ማቆም አድማን አልታገስም፡፡ እኔ የሥራ ማቆም አድማ ባደርግና ደሞዝ አልፈርምም ብል ሰራተኞቼ ምን ይሉኛል?
አላን ቦንድ
(አውስትራሊያዊ የቢዝነስ ሥራ አስፈፃሚ)
ህገ-መንግስታዊው መንግስት ጥቃት እየተሰነዘረበት ነው - አጠቃላይ አድማው ለፓርላማው ፈተና ነው፡፡ የሥርዓት አልበኝነትና የጥፋትም ጎዳና ነው፡፡
ስታንሌይ ባልድዊን
(የእንግሊዝ ጠ/ሚኒስትር)
ሁላችንም ካልተባበርነው በቀር ማንም ሰው አገርን ሙሉ ሊያሸብር አይችልም፡፡
ኢዲ ሙሮው
(አሜሪካዊ ጋዜጠኛ)
በሌላው ላይ የማዘዝ ሥልጣን ያለው ሰው ሁሉ ጨቋኝ ነው፡፡
ፍራንሲስኮ ፒዋይ ማርጋል
(ስፔናዊ ፖለቲከኛና ደራሲ)
ሰዎች ቄሳሮችንና ናፖሊዮኖችን ማምለክ እስካላቆሙ ድረስ ቄሳሮችና ናፖሊዮኖች መከራ ሊያበሏቸው መነሳታቸው አይቀርም፡፡
አልዶስ ሁክስሌይ
(እንግሊዛዊ ደራሲና ወግ ፀሐፊ)
ራሱን እንዲወደድ ማድረግ ያቃተው፣ ራሱን እንዲፈራ ማድረግ ይሻል፡፡
ዣን ባንቲስት ራሲን
(ፈረንሳዊ ፀሐፌ ተውኔት)
ጭቆና ሁልጊዜ ከነፃነት የተሻለ የተደራጀ ነው፡፡
ቻርልስ ፒሬ ፔለጉይ
(ፈረንሳዊ ፀሐፊና ገጣሚ)
በጨቋኝ ሥርዓት ውስጥ ከማሰብ ይልቅ መተግበር ይቀላል፡፡
ሃና አሬንድት
(ትውልደ - ጀርመን አሜሪካዊ ፈላስፋና የታሪክ ምሁር)
ሰውየውን እየጨቆንክ ለታሪኩ፣ ለሰዋዊነቱና ለስብዕናው ዕውቅና መስጠት አትችልም፡፡ ስለዚህ እነዚህን ነገሮች በዘዴ ከእሱ ላይ መውሰድ አለብህ፡፡ እናም ይሄ ሰው በታሪክ ውስጥ ያለውን ሚና በተመለከተ በመዋሸት ትጀምራለህ፡፡
ጆን ሄንሪክ ክላርክ
(አሜሪካዊ የታሪክ ባለሙያና የትምህርት ሊቅ)
ሁሉም ዘመናዊ አብዮቶች የተጠናቀቁት የመንግስትን ሥልጣን በማጠናከር ነው፡፡
አልበርት ካሙ
(ትውልደ - አልጀርያ ፈረንሳዊ ደራሲና ድራማ ጸሃፊ)

 

  • .  ተመራቂ ወጣቶችን ወደ ቢዝነስና ወደ ሥራ ፈጠራ ለማነሳሳት የሚጣጣር መንግስት፤ የቢዝነስ ሰዎች “አጭበርባሪ፣ ስግብግብና ኪራይ ሰብሳቢ ናቸው” እያለ ያንቋሽሻቸዋል። እዚያው በዚያው የራሱን ጥረት ራሱ ያመክነዋል።
  • .   አገሪቱ ከድህነት ተላቃ ማደግ የምትችለው በትርፋማ የቢዝነስ ሰዎች ጥረት ነው የሚል መንግስት፤ የራሱን ንግግር ራሱ ያፈርሰዋል። ትርፍ ለማግኘት መስራትን ያብጠለጥላል - “የማስቲካና የከረሜላ አስመጪ” እያለ።
  • .  ሕይወቱ እንዲሻሻልና ኑሮው እንዲበለፅግ የሚመኝ ብዙ ሰው፤ ራስ ወዳድነትን ሳይሆን መስዋእትነትን፣ ከትርፋማነት ይልቅ ምፅዋትን ያወድሳል። ራሱን ያልወደደና ትርፋማነትን ያላከበረ ሰው እንዴት ሕይወቱን ያሻሽላል?
  • .  መንግስትን የማያምን የአገሬ ሰው፤ “ነጋዴዎች፣ የሸቀጥ እጥረትንና የዋጋ ንረትን ይፈጥራሉ” በሚለው ውንጀላ መንግስትን ሙሉ ለሙሉ ያምናል - እጥረት የተባባሰው በመንግስት የተያዙት ስኳር፣ ዘይትና ስንዴ ላይ ቢሆንም።


በአንድ በኩል፤ ስለ ብቃትና ስኬት ማውራት
እየተለመደ መጥቷል - ቢዝነስና ትርፋማነት፣ ሥራ ፈጠራና ኢንዱስትሪ፣ ሃብት ፈጠራና ብልፅግና... ዘወትር ስማቸው እየተደጋገመ ይነሳል።  
በሌላ በኩል ደግሞ፤ ስኬት፣ ትርፋማነትና ሃብት ፈጠራ እየተንቋሸሹ፣ ምስኪንነት፣ ምፅዋትና አገልጋይነት ሲሞገሱና ሲወደሱ እንሰማለን። አዲስ ነገር አይደለም። “የዚህ አለም ደስታና ብልፅግና ረብ የለሽ አላፊና ረጋፊ ነው” ከሚለው ጥንታዊ የውድቀት ባሕልና አስተሳሰብ አልተላቀቅንም። ይህም ብቻ አይደለም። በዚሁ ኋላቀርነት ላይ፤ ባለፉት አርባ ዓመታት ሌላ መርዝ ተጨምሮበታል። “ከራሴ በፊት ለሰፊውና ለድሃው ሕዝብ መስዋእት ልሁን” የሚል የሶሻሊስቶች መፈክር፤ “ከራሴ በፊት ለእናት አገሬ፣ ለብሔር ብሔረሰቤ” የሚል የፋሺስቶች መዝሙር፣ ይሄውና አሁንም ድረስ የብዙ ኢትዮጵያውያንን ስሜት ይኮረኩራል።
ምናለፋችሁ! ሁሉም ነገር የተቀየጠ ሆኗል፡፡ ስለ ብቃትና ስለ ስኬት የሚያወራ ሰው፤ ዞር ብሎ ምስኪንነትንና መስዋዕትነትን ያዳንቃል። ሃብት ፈጠራንና ቢዝነስን አበረታታለሁ የሚል መንግስት፤ ዞር ሳይል ባለሃብቶችን በሰበብ አስባቡ እየወነጀለ ቁምስቅላቸውን ያሳያቸዋል፤ “የሃብት ክፍፍል” እያለ በፖለቲካ ቋንቋ ጥንታዊውን የምፅዋት አምልኮ ይሰብካል። ሁለት ሱሪ ያለው አንዱን ያካፍል እንዲሉ፡፡
እናላችሁ፣ ራስን ጠልፎ የመጣል አባዜ የበረከተበት ግራ የተጋባ ዘመን ላይ ነው ያለነው። እየገነቡ የማፍረስ በሽታ! ብልፅግናን እየፈለጉ ራስ ወዳድነትን የማብጠልጠል ልክፍት! ይህንን በግልፅ የሚመሰክሩ አራት የሰሞኑ ዜናዎችን እጠቅስላችኋለሁ።

1. ተመራቂዎች ቢዝነስን ወይም አገልጋይነት?
ዘንድሮ ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የሚመረቁ ከ50ሺ በላይ ወጣቶች፣ ከመንግስት ሳይጠብቁ፤ በራሳቸው መንገድ ሕይወታቸውን የሚያሻሽል ሥራ (ቢዝነስ) እንዲፈጥሩ ምክርና ማሳሰቢያ ከመንግስት ባለስልጣናት ሲጎርፍላቸው ሰንብቷል። ቀላል ምክር አይደለም። ጉዳዩ፤ የድህነትና የብልፅግና፤ የሞትና የሕይወት ጉዳይ ነው - ለእያንዳንዱ ወጣት። ስንቱ የጨነቀው ወጣት፣ ድንበርና እየዘለለ፣ ኬላ እየሰበረ፣ የበረሃውን ንዳድ የባህሩን ውርጭ እያቆራረጠ የሚሰደደው ለምን ሆነና! ጉዳዩ፤ የኢኮኖሚ እድገትና የኢኮኖሚ ቀውስ ጉዳይ ነው - ለመንግስት። በየአቅጣጫው በርካታ አገራት ሲተራመሱ የምናየው፣ በርካታ መንግስታት ሲቃወሱና ሲፈናቀሉ የምንመለከተው ለምን ሆነና! የጎሰኝነት ጡዘትና የሃይማኖት አክራሪነትን ጨምሮ፤ ከዘመናችን ሶስት ዋና ዋና ቀውሶች መካከል አንዱ፤ ወጣቶችን ተስፋ የሚያስቆርጥ የኢኮኖሚ ቀውስ ነው - በገናና የሚፈጠር የቅይጥ ኢኮኖሚ ቀውስ፡፡ እናም፤ ተመራቂ ወጣቶች ለስራ ፈጠራና ለቢዝነስ እንዲነሳሱ፣ ከመንግስት በኩል ምክርና ማሳሰቢያ እየተደጋገመ ቢሰነዘር አይገርምም። ብልህነት ነው፤ የህልውና ጉዳይ ስለሆነ።
ታዲያ፤ ተመራቂዎቹ ወጣቶች ይህንን እጅግ ትልቅ ምክር ሰምተው፤ የራሳቸውን ቢዝነስና ንግድ ቢፈጥሩ፣ አድናቆትና ክብር ያገኛሉ ማለት አይደለም። ጉዳዩ የሕይወትና የሞት፣ የብልፅግናና የቀውስ ጉዳይ ቢሆንም ያን ያህል ክብደት አይሰጠውም።
እንደ ትልቅ ነገር ተቆጥሮ ክብር የተለገሰውና በስፋት የተለፈፈው ጉዳይ ምን እንደሆነ ልንገራችሁ። በመቶ ሺ የሚቆጠሩ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፤ በክረምት ወራት ጊዜያቸውን ለህዝቡና ለአገር መስዋእት በማድረግ፣ ለበጎ አድራጎት ስራ ይሰማራሉ የሚል ዜና አልሰማችሁም?
በእርግጥም፤ የከፍተኛ ትምህርት አላማ፤ የራሳቸውን ቢዝነስ እየከፈቱ ራሳቸውን የሚጠቅሙ ተመራቂዎችን ማፍራት ሳይሆን፤ አገሪቱን በተለያዩ ሙያዎች የሚያገለግል የሰው ሃይል ማፍራት ነው  - የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ። ያ ሁሉ የዩኒቨርስቲ ተማሪ፤ በክረምት ወራት መስዋእትነት፣ አንዳች ጠብ የሚል ቁም ነገር አይሰራ ይሆናል። ዋናው ነገር፤ ለየራሳቸው በሚጠቅም ስራ ላይ ሳይሰማሩ የክረምቱን ጊዜ (መስዋእት ማድረጋቸው) ማቃጠላቸው ነው። ቢረባም ባይረባም፤ ለቢዝነስ ሳይሆን ለአገልጋይነት መሰማራታቸው ነው - አድናቆትን የሚያተርፍላቸው።
በአጭሩ፤ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፣ የመንግስት ጥገኛ ከመሆን ይልቅ በስራ ፈጣሪነት ሕይወታቸውን እንዲያሻሽሉ መንግስት ማሳሰቢያ ሲሰጥ መሰንበቱ ብልህነት ነው። ተመራቂዎች ሥራ መፍጠር ካልቻሉ፤ ሥራ አጥነትና ተስፋቢስነት እየተስፋፋ አገሪቱ ልትቃወስ ትችላለቻ። ይህን አደጋ በመገንዘብ፤ ተመራቂዎች የየራሳቸውን ሕይወት ለማሻሻል ከሁሉም በላይ ለሥራ ፈጠራ ቅድሚያ መስጠት እንዳለባቸው ሲመክር የሰነበተ መንግስት፤ ያንን ምክር ለማምከን ሲጥር መሰንበቱ ነው ችግሩ። የአገርና የህዝብ አገልጋይ መሆን ከሁሉም የላቀ ክብር እንደሚገባው በመግለፅ፣ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የክረምት ጊዜያቸውን “ለበጎ አድራጎት ሥራ” መስዋእት እንዲያደርጉ መንግስት አሰማርቷቸዋል። ራስን ጠልፎ የሚጥል ቅይጥ አስተሳሰብ ይሉሃል ይሄ ነው፡፡

2. የመንግስት የጅምላ ንግድ - ነጋዴዎችን ለማበረታታት ወይስ ለመጣል?
መንግስት፣ ሶስተኛውን የጅምላ ንግድ ማዕከል በመርካቶ ሲከፍት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ ዋና አማካሪ አቶ ነዋይ ገብረአብ፤ የግል ባለሃብቶች ወደ ዘመናዊ የጅምላ ንግድ እንዲሸጋገሩ ለማሳየትና ለማነሳሳት ይጠቅማል ብለዋል። የጅምላ ንግድ በመንግስት ሳይሆን በባለሃብቶች እንዲካሄድ እንፈልጋለን ሲሉም ተናግረዋል። (አማካሪው ለምን እንዲህ አሉ? የባለሃብቶች የግል ኢንቨስትመንት፣ ኢኮኖሚውን የሚያንቀሳቅስ ዋነኛ ሞተር ነው። የቢዝነስ ሰዎች ሃብትን ይፈጥራሉ፤ ራሳቸውን ለመጥቀምና ትርፍ ለማግኘት ሲጣጣሩ፤ ሌላውም ሰው ይጠቀማል በሚል እምነት ነው)።
በሌላ በኩል እስከአሁን ሶስት የመንግስት የጅምላ ንግድ ማዕከላት እንደተከፈቱና ተጨማሪ ማዕከላትን በመክፈት አገልግሎቱ እንደሚስፋፋ የገለፁት የንግድ ሚኒስትር፤ ዋነኛ አላማው በነጋዴዎች አማካኝነት የሚፈጠረውን የሸቀጥ እጥረትና የዋጋ ንረት መከላከል እንደሆነ አስታውቀዋል። (ለምን የቢዝነስ ሰዎችን መወንጀል አስፈለገ? መንግስት በገፍ የብር ኖት ከማሳተም ከተቆጠበ ወዲህ የዋጋ ንረት ረግቧል - ከ2003 ወዲህ ። መቼም ቢሆን፣ የዋጋ ንረት የሚፈጠረው በመንግስት እንጂ በነጋዴዎች ወይም በቢዝነስ ሰዎች አማካኝነት አይደለም። እንዲያም ሆኖ፤ በተገኘው ሰበብ የግል ቢዝነስንና ንግድን መኮነን የአገራችን ነባር ባህል ነው። እናም መንግስት፣ “የግል ቢዝነስ፣ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ዋነኛ የቀውስ አደጋ ነው። የቢዝነስ ሰዎች፤ ለአገር ልማት ሳይሆን ትርፍ ለማግኘት ይሰራሉ” በሚል እምነት ዘወትር ተመሳሳይ ውንጀላ ያዘንብባቸዋል)

3. ፎቀቅ ያላለውን ኢንዱስትሪ ለማነቃቃት - ባለሃብቶችን ማነሳሳት ወይስ ማብጠልጠል?
ባለሃብቶች ከንግድ ቢዝነስ ባሻገር፣ ወደ ማምረቻ (ወደ ማኑፋክቸሪንግ) የኢንዱስትሪ ቢዝነስ እንዲገቡ ለማነሳሳት፣ የንግድ እና የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በወዲያኛው ሳምንት ለሁለት ቀናት ገለፃ ሲሰጡ ውለዋል። ለምን? የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የኢንዱስትሪ ስትራቴጂ በሚል ያዘጋጁት ሰነድ እንደሚለው፤ በግል ኢንቨስትመንት እንጂ በሌላ መንገድ ስኬታማና ትርፋማ ፋብሪካዎችን ማስፋፋት አይቻልም። እናም ፋብሪካዎች በትርፋማነት እንዲስፋፉና እንዲያድጉ፤ የስራ እድሎች በብዛት እንዲከፈቱ ከተፈለገ፤ የቢዝነስ ሰዎች በዚሁ መስክ እንዲሰማሩ ማግባባት ያስፈልጋል - የተለያዩ እንቅፋቶችንና መሰናክሎችን በማስወገድ።
የማኑፋክቸሪንግ ቢዝነስ፤ አርቆ አሳቢነትንና ፅናትን፣ ለአመታት የሚዘልቅ ጥረትንና የፈጠራ ትጋትን ይጠይቃል። ይህንን የማሟላት ችሎታ ያላቸው ደግሞ የመንግስት ቢሮክራቶች ሳይሆኑ የቢዝነስ ሰዎች ናቸው። በወዲያኛው ሳምንት የተዘጋጀው ገለፃም ከዚሁ እምነት ጋር ይያያዛል። የመንግስት ባለስልጣናት እንዲህ አይነት እምነት ከያዙ፤ “እውነትም ለቢዝነስ ስራና ለቢዝነስ ሰዎች ትልቅ ክብር አላቸው” ያስብላል። ግን፤ ወዲያውኑ አፍርሰውታል።
አክብሮትን ሳይሆን ተቃራኒውን ስሜት ለማሳየት ጊዜ ያልፈጀባቸው የመንግስት ባለስልጣናት፤ “የአገራችን ባለሃብቶች፣ በአጭር ጊዜ እና በቀላሉ ከፍተኛ ትርፍ ማግኘት ይፈልጋሉ” ሲሉ ከዘለፋ ወዳልተናነሰ ቅኝት የተሸጋገሩት በዚያው ገለፃ ላይ ነው። የንግድ ስራ ቀላል ነው? ቀላል ቢሆን፣ ለምን የመንግስት ባለስልጣናትና ቢሮክራቶች በንግድ ስራ አይሳካላቸውም? ለምን ደርግ አልተሳካለትም፣ ዛሬም መንግስት የገባበት የንግድ ስራ በሙሉ፤ በሙስናና በሸቀጥ እጥረት ሲበላሽ የምናየውኮ አለምክንያት አይደለም። የስንዴ እጥረት፣ የዘይት እጥረት፣ የስኳር እጥረት... እነዚህ በመንግስት የተፈጠሩ ችግሮች ሁሉ፤ የንግድ ቢዝነስ ቀላል እንዳልሆነ የሚመሰክሩ ናቸው። የመንግስት ባለስልጣናት ይህንን የአደባባይ እውነት ለማገናዘብ ፍቃደኛ አይመስሉም።
ይልቁንስ ትርፋማነትንና ቢዝነስን የሚያንቋሽሽ ነባር የአገራችንን ባህል ይዘው ማራገብንና መዛትን መርጠዋል። የቢዝነስ ሰዎች በተለመደው የንግድ ሥራ “ኪራይ ሰብሳቢ” ሆነው ለመቀጠል እንጂ ወደ አምራች የኢንዱስትሪ ቢዝነስ ገብተው “ልማታዊ ባለሃብት” ለመሆን የማይፈልጉ ከሆነ፤ ብድር አያገኙም ሲሉ ባለስልጣናት ተናግረዋል። “የቢዝነስ ሰዎች፣ በጥረት ሃብት መፍጠር አይፈልጉም። በቀላሉ ትርፍ ለማጋበስ እንጂ ለአገር ልማት አስተዋፅኦ የማድረግ ሃሳብ የላቸውም - ከረሜላና ማስቲካ አስመጪ ሁላ!” ...
ራስን ጠልፎ መጣል፣ እየገነቡ ማፍረስ ይሏል ይሄው ነው ብሎ ማንኮታኮት ነው፤ የቅይጥ ኢኮኖሚ ባህርይ፡፡

4. የመንግስት ሰራተኞች የደሞዝ ጭማሪ - የዋጋ ንረትን ይፈጥራል ወይስ አይፈጥርም?
ለመንግስት ሰራተኞች ደሞዝ ስለተጨመረ፣ የዋጋ ንረት እንደማይከሰት የገለፁት የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር፤ የደሞዝ ጭማሪው በጥናት ላይ የተመሰረተና በበጀት የተያዘ ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል - ለደሞዝ ጭማሪ ተብሎ የብር ኖት ህትመት በገፍ እንደማይካሄድም ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝም እንዲሁ፣ ተመሳሳይ መከራከሪያ በማቅረብ፣ የዋጋ ንረት የሚፈጠርበት አንዳችም ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የለም ብለዋል። በእርግጥም፤ መንግስት የብር ኖቶችን በገፍ ከማሳተም እስከተቆጠበ ድረስ፤ የዋጋ ንረት አይፈጠርም። ትክክል ነው። እንዲያም ሆኖ፣ በዚህችው አጋጣሚ፣ የቢዝነስ ስራንና የቢዝነስ ሰዎችን ሳይወነጅሉ ለማለፍ አልቻሉም። “ስግብግብ ነጋዴዎች የዋጋ ንረት እንዳይፈጥሩ ክትትልና ቁጥጥር ይካሄዳል፤ ሕጋዊ እርምጃ ይወሰዳል” በማለት ደጋግመው ተናግረዋል።
ዜጎች በሥራ ፈጠራና በምርታማነት ኑሯቸው እንዲሳካ፣ የቢዝነስ ሰዎች በትርፋማነት ኢንዱስትሪ እያስፋፉ እንዲከብሩ፤ በአጠቃላይ ለሃብት ፈጠራና ለብልፅግና ከፍተኛ ዋጋ እንደሚሰጥ የሚገልፅ መንግስት፤ የቢዝነስ ስራንና የቢዝነስ ሰዎችን ማጣጣል መደበኛ ስራው ሲሆን ምን ይባላል? “ራስን ጠልፎ የመጣል አባዜ” አይደለምን?
“ጥቃቅንና አነስተኛ” በሚል የተለያዩ የቢዝነስ ሥራዎችን የጀመሩ በርካታ ወጣቶች፣ “ገበያ አጣን” በማለት በተደጋጋሚ ለመንግስት አቤቱታ እንደሚያቀርቡ ሳታውቁ አትቀሩም፡፡ መንግስትም፤ “የገበያ ትስስር እፈጥርላችኋለሁ” እያለ በርካታ ፕሮጀክቶችን ያለጨረታ ለዚህኛውና ለዚያኛው ሲቸር ቆይቷል፡፡ ግን ለሁሉም ጥቃቅን ተቋማት ከዓመት ዓመት ችሮታ ማዳረስ አይቻልም፡፡ “የገበያ ትስስር እፈጥርላችኋለሁ” የሚለው ፈሊጥ እንደማያዋጣ  ቀስ በቀስ የተገነዘቡ ባለስልጣናት አሁን አሁን የሚሰጡት ምላሽ፤ “ከመንግስት ችሮታ የምትጠብቁ ጥገኞች መሆን የለባችሁም” የሚል ሆኗል።
እውነትም፣ የቢዝነስ ሰዎች እንጂ ቢሮክራቶች ለዘለቄታው የሚያዋጣ የገበያ ትስስር የመፍጠር አቅም የላቸውም። የቢዝነስ ሰዎች ገበያ የሚያገኙትና ትርፋማ የሚሆኑት ለምንድነው? አንዴ ሁለቴ፣ ይሄንን ወይም ያንን በማጭበርበር ለማምለጥ የሚሞክሩ የቢዝነስ ሰዎች መኖራቸው አያጠራጥርም። ነገር ግን፣ ብዙም አይራመዱም። ስኬታማ መሆን የሚችሉት፣ በተወዳዳሪነት ብቃት ነው።  የመንግስት ባለስልጣናት ይሄንን አያጡትም። “ጥቃቅንና አነስተኛ” የቢዝነስ ተቋማትን ለሚመሰርቱ ወጣቶችም ይህንኑን ሲነግሯቸው ሰምተናል - “በጥራትና በዋጋ ተወዳዳሪ የሆነ ምርት ስታቀርቡ ነው ገበያ በማግኘት ትርፋማና ስኬታማ መሆን የምትችሉት” በማለት።
ይሄ ምክር፣ አማራጭ የሌለው ትክክለኛና የሚያዋጣ ምክር ነው። በሌላ አነጋገር፤ ዋጋ በማናር ለማትረፍ የሚሞክር ነጋዴ፤ ገበያተኛ እየሸሸው ይከስራል እንጂ አይሳካለትም። በሌላ አነጋገር፣ ነጋዴዎች የዋጋ ንረትን መፍጠር አይችሉም። ይህንን የሚያውቁና የሚናገሩ ባለስልጣናት፤ ዞር ብለው “ነጋዴዎች የዋጋ ንረትን ይፈጥራሉ” የሚል ውንጀላ ሲሰነዝሩ ምን ይባላል? በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ለተሰማሩ ወጣቶች የሰጡትን ምክር፣ መልሰው ይንዱታል። “እንዳሻችሁ ዋጋ በማናር ገበያ ማግኘትና ትርፋማ መሆን ትችላላችሁ” የሚል የውሸት ምክር እንደመስጠት ቁጠሩት - እውነተኛውን ምክር የሚያፈርስ።   
በአጠቃላይ፤ ዛሬ ዛሬ ለወሬ ያህል ደግ ደጉን ማውራት ተጀምሯል። ብቃትና ስኬት፣ ትርፋማነትና ብልፅግና፣ ምርታማነትና ስራ ፈጠራ፣ መጣጣርና የራስን ሕይወት ማሻሻል የሚሉ ቃላት ባገሬ ሰዎች አንደበት ዘንድ እየተዘወተሩ ነው። የመንግስት ባለስልጣናትም እንዲሁ፣ ኢንቨስትመንትን መሳብ፣ ኢንዱስትሪን ማበረታታት፣ የገበያ ተወዳዳሪነትን ማሳደግ እያሉ ሲናገሩ እንሰማለን። ጥሩ ነው። ግን “ወሬ ብቻ ሆኖ ይቀራል፡፡ የስኬት ወሬ፣ በተግባር የማይሳካው፤ አብዛኛው የአገሬ ሰውም ሆነ የመንግስት ባለስልጣናት፤ በገዛ አንደበታቸው ለሚናገሩት “የስኬት ሃሳብ”፤ እምብዛም ክብር ስለሌላቸው ነው። ከብቃትና ከስኬት ይልቅ፤ አቅመ ቢስነትንና ምስኪንነትን፤ ከትርፋማነትና ከብልፅግና ይልቅ ምፅዋትንና ችግር መጋራትን፤ ከስራ ፈጠራና ሕይወትን ከማሻሻል ይልቅ መስዋእት መሆንና አገልጋይነትን ያደንቃሉ - ያገሬ ሰውና ያገሬ መንግስት።
ከ“ትርፋማነት” እና ከ“ምፅዋት” መካከል የትኛውን ነው “በጎ አድራጎት” በማለት የምናሞግሰው? ያገሬ ሰው በአብዛኛው፤ የ“ምፅዋት” አወዳሽ ነው - “ሁለት ጫማ ያለው አንዱን ይመፅውት” ይባል የለ! መንግስትንም ብታዩት፣ ከዚህ የተለየ አይደለም።
መንግስት አገሬውን ይመስላል። መቼም፤ ለኢትዮጵያ ተብሎ፣ ከሌላ ፕላኔት ልዩ መንግስት አይመጣም። ያገራችንን መንግስትና ገዢ ፓርቲ ተመልከቱ። የመንግስትን ስልጣን ለመያዝ የሚፈልጉ ሌሎች ፓርቲዎችንና ፖለቲከኞችንም ጠይቋቸው። ባትጠይቋቸውም ይነግሯችኋል። ለድሆች የቆሙና “ለዝቅተኛው ሕብረተሰብ” የወገኑ መሆናቸውን በኩራት የሚናገሩት የአገራችን ፓርቲዎች፣ የምፅዋት አድናቂዎች ናቸው - ከራሳቸው ኪስ በማይወጣ ገንዘብ ድሆችን በመደጎም ተአምረኛ ለውጥ እናመጣለን ብለው የሚያልሙ።
ከሁሉም ፓርቲዎች አፍ የማይጠፋ፣ እንደ ፀሎት ቀን ከሌት የሚደጋግሙት “እጅግ የተከበረ ቅዱስ መፈክር” ቢኖር፤ “የሃብት ክፍፍል” የሚለው ፈሊጥ ነው። ያው “ሁለት ልብስ ያለው አንዱን ይመፅውት” ከሚለው ስብከት ጋር ይመሳሰላል። ግን ይብሳል። “ምፅዋቱ” በፈቃደኝነት የሚፈፀም ሳይሆን በሕግ የታወጀ ግዴታ እንዲሆን ያደርጉታል። ለነገሩ፤ አቅመቢስነትንና ምስኪንነትን፤ ምፅዋትንና ጥገኝነትን አስበልጦ የመውደድና የማምለክ ጉዳይ ብቻ አይደለም። በተቃራኒው፤ ብቃትንና ስኬትን፣ ትርፋማነትንና ብልፅግናን የማጣጣል፤ ከዚያም አልፎ የማንቋሸሽና የማውገዝ ዝንባሌ ይታከልበታል። “ራስ ወዳድነት”ን እንደ ስድብና ኩነኔ የምንቆጥረው ለምን ሆነና?  “ትርፍ ለማግኘት የሚሯሯጡ አጭበርባሪና ስግብግብ ነጋዴዎች” የሚለው የአገራችን የተለመደ አባባል የዚህ ዝንባሌ መለያ ታፔላ ነው። “የሃብት ልዩነት ሰፍቷል” የሚለው ውግዘትም እንዲሁ።        
መንግስት፤ የሙያና የቢዝነስ ሰዎች፣ በየመስኩ ፋብሪካ እየከፈቱ የኢንዱስትሪ ምርትን እንዲያስፋፉ ይመኛል። ምኞቱ እውን ሊሆን የሚችለው፤ የቢዝነስ ሰዎች ስኬታማና ትርፋማ ሲሆኑ ነው። ነገር ግን፤ የቢዝነስ ሰዎች ከሌላው ሰው የበለጠ ሃብት ማፍራታቸው መንግስትን አያስደስትም። “የሃብት ልዩነት”ን በደስታ ለመቀበል ፈቃደኛ አይደለም። በደስታ ይቅርና፤ በዝምታ ወይም በቅሬታ ለመቀበልም አይፈልግም። “ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል” የሚለው ነገር አለ።
በፖለቲከኞቹ ቋንቋ “ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል” ማለት፤ ከታታሪ የፈጠራ ሰው (ማለትም ከስኬታማና ከትርፋማ ሰው) ሃብት በመውሰድ፤ ሃብትን በኪሳራ ለሚያባክንና ሃብትን ለማያፈራ ሰው መስጠት ማለት ነው። “ፍትሃዊ” ማለት፤ ሁሉንም ሰው እኩል ለማድረግ ፈጣን ሯጮችን ማንቋሸሽ፤ ቀን ከሌት ሲሰሩም፤ “አሸናፊ ለመሆን የሚመኙ በስግብግቦች” እያልን መወንጀል፤ ስኬታማዎች ወደ ፊት እንዳይራመዱ ቅልጥማቸውን ሰብሮ ማሳረፍ፣  ፈጣን ሯጭ ያልሆነውም ሰው እንዳይጣጣር ማባበል እንደማለት ነው።
አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ከመንግስት የተለየ አስተሳሰብ የለውም። ብቃትንና ስኬትን ከምር የሚፈልጉ ሰዎች፤ በብቃት የላቀ ስኬታማ ሰው ሲያጋጥማቸው በአድናቆትና በክብር ያሞግሱታል፤ በአርአያነቱም መንፈሳቸውን ያነቃቃሉ። ብዙ የአገሬ ሰዎች ግን፣ ቀልባቸው የሚማረከው አቅመቢስና “አለም በቃኝ” ብሎ ራሱን የጣለ ምስኪን ሲያጋጥማቸው ነው። ትርፋማነትንና ብልፅግናን የሚፈልጉ ሰዎች፤ ሃብትን በማፍራት የበለፀገ ትርፋማ የቢዝነስ ሰው ሲያጋጥማቸው፤ ውስጣቸው በአድናቆት ይሞላል፤ ታሪኩን ለማወቅ ይጓጓሉ። አብዛኛው የአገሬ ሰው ግን፤ የቢዝነስ ኩባንያን ሳይሆን የእርዳታ ድርጅትን፣ ለትርፍ የተቋቋመ ፋብሪካን ሳይሆን በበጎ አድራጎት የተተከለ ችግኝን በማስበለጥ እንደ ቅዱስ ነገር ያያል።
በአጭሩ፤ በነባር ተራ ቃላት፣ በተድበሰበሱ ምሁራዊ ሃረጋት ወይም በተሰለቹ ፖለቲካዊ አባባሎች ልዩ ልዩ ቀለም ብንቀባውም፤ አብዛኛው የዘመናችን አስተሳሰብ ከጥንታዊው የኋላቀርነት ባህል ብዙም አይለይም። “የዚህ አለም እውቀትና ሙያ እንደ ብናኝ ክብደት የሌለው፤ የዚህ አለም ደስታ እንደ ጤዛ ውሎ የማያድር፤ የዚህ አለም ስኬትና ብልፅግና እንደ ሸክላ ተሰባሪ፤ የዚህ አለም ኑሮና ምቾት እንደ ቅጠል ረጋፊ” ... ከሚል የውድቀት ቅኝት አልተላቀቅንም። ራሳችንን ጠልፈን የመጣል አባዜ የተጠናወተንም በዚህ ምክንያት ነው። ይህንን ካስወገድን፤ የብቃትና የስኬት፣ የሥራ ፈጠራና የትርፋማነት፣ የሃብት ፈጠራና የብልፅግና ጉዟችንን የሚያሰናክል ከአቅም በላይ የሆነ እንቅፋት አይኖርብንም። ለነገሩ ብዙም ሊያከራክረን አይገባም ነበር፡፡ ምፅዋት የሚኖረው እኮ፣ በቅድሚያ የሃብት ፈጠራ ሲኖር ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ በሃገራችን የብሄር እውቅና ጥያቄ ከሚያነሱ ህዝቦች መካከል በአማራ ክልል ጎንደርና አካባቢዋ ነዋሪ የሆኑት “ቅማንቶች” ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ይህን የቅማንቶች ታሪክና የብሄር ጥያቄ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አደባባይ ይዘው ብቅ ያሉት ደግሞ ከኒውዮርክ “ዩኒቨርሳል ፒስኮርፕ ኮርፖሬሽን” የሰላም አምባሳደርነት ማዕረግ ያገኙት አቶ ነጋ ጌጡ ናቸው፡፡ “የአማራ አቀፍ ልማት ማህበርን ካቋቋሙት አንዱ ነኝ” የሚሉትና በጎንደር የፋርማሲ ባለቤት የሆኑት አቶ ነጋ፤ ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ የቅማንትን ብሄረሰብ ለማስተዋወቅና የብሄር ጥያቄያቸው እንዲመለስ ብዙ መስዋዕትነት እንደከፈሉ ይናገራሉ፡፡ ምላሽ ለማግኘት ያልገቡበት የመንግስት መዋቅር እንደሌለም የሰላም አምባሳደሩ ይገልፃሉ፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት የብሄረሰቡን የእውቅና ጥያቄ ተቀብሎ ከመረመረ በኋላ በድጋሚ እንዲጠና ትዕዛዝ ማስተላለፉን አቶ ነጋ ይናገራሉ፡፡ “የብሄረሰቡ ጥያቄ መቼም ተዳፍኖ አይቀርም፤ ቅማንት ቅማንት ነው፤ ማንም አይሽረውም” ባይ ናቸው፡፡
የአዲስ አድማስ ከፍተኛ ሪፖርተር አለማየሁ አንበሴ  
ለስራ ጎንደር በቆየበት ወቅት ከአቶ ነጋ ጌጡ ጋር በብሄረሰቡ ማንነት፣ ባህልና ቋንቋ ዙሪያ አውግቷል፡፡  


እስቲ ስለቅማንት ብሄረሰብ ማንነት በዝርዝር ይንገሩኝ?
የቅማንት ብሄረሰብ ቀደምት ህዝብ ከሚባሉት ውስጥ አንዱ ነው፡፡ መገለጫው በኛ በቅማንቶች አባት፣ እሚታ፣ አያት፣ ቅድመ አያት - ቅማንት - ምንዥላት - እንጃለት ብለን 7ኛ ቤት ድረስ ይሄዳል። 6ኛው ዙር ምንዥላት የሚባለው አሁን ጠፍቷል፡፡ አሁን ያለው የመጨረሻው ቅማንት ነው፡፡ እነዚህ ከአባት ተጀምሮ ወደ ላይ የሚጠሩት የዘር ተዋረዶች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያዊ ህብረተሰብ “እሚታ”ን አያውቀውም፡፡ ስም ከነአያት እየተባለ ነው የሚፃፈው፡፡ በኛ ግን ከአባት ቀጥሎ እሚታ፣ ከእሚታ ቀጥሎ አያት ይከተላል፡፡ አሁን እኔ ስጠራ ነጋ ጌጤ ለምለሙ ተስፋዬ ነው፡፡ እናንተ ግን ስትጠሩኝ ነጋ ጌጤ ተስፋዬ ብላችሁ ነው፡፡ ምክንያቱም እሚታዬን ፃፍ አላላችሁኝም፡፡ በብሄረሰቡ አጠራር የአባት ስም መጀመሪያ ይሆንና የልጅ ስም ይከተላል፡፡ ለምሳሌ የእኔ “ጌጤ ነጋ” ነው በብሄረሰቡ አጠራር፡፡
እንግዲህ ቅማንት ማለት ስንተረጉመው፤ “ከመንታ” ማለት ነው፡፡ ከመንታ ማለት “አንተ ካም ነህ” ማለት ነው፡፡ በመፅሃፍ ቅዱስ የምናውቃቸው ኖህ፣ ሶስት ልጆች አሏቸው - ሴም፣ ያፌት፣ ካም ይባላሉ፡፡ አፍሪካውያን የካም ልጆች ናቸው። የካም ልጆች ደግሞ ኩሽ፣ ምዝራይብ፣ ፉጥ እና ከነአን ናቸው፡፡ ከዚህ መሃል የኛን ዘር የምናወጣው ከከነአን ልጆች ነው፡፡ አራዲዮን - አደረኪን ወለደ። አደረኪ ሶስት ሚስቶችን አገቡ፡፡ አንደኛዋ ሚስታቸው አንዛኩና ትባላለች፣ ሁለተኛዋ ሚስታቸው ፌይኖባኩላ፣ ሶስተኛዋ ሚስታቸው ሰሜንድራ ትባላለች፡፡ ከአንዛኩና ቅማንትን፣ አገውን እና ቢሌንን (ኤርትራ ውስጥ ያሉ) ይወለዳሉ፡፡ ከሁለተኛ ሚስታቸው ካይላ፣ ሞረትን፣ አርጎባን እና ጋፋትን ይወልዳሉ፣ ከሶስተኛ ሚስታቸው ስራሁን፣ አከላጉዙ፣ ሐማስን፣ ሞንአሞርን፣ ቤጃን ይወልዳሉ። ከእነዚህ ሶስት እናቶች የተወለዱ ልጆች ታላቁን አባት ሃገር የሚባለውን ይመሰርታሉ፡፡ “ታላቁ አባት ሃገር” የሚባለው በቅማንትኛ አቢሲኒያ ነው። አቢሲኒያ ማለት በቅማንትኛ “አባት ሃገር” ማለት ነው፡፡
እንግዲህ ይሄ ሁሉ የዘረዘርነው ዘር እየተዋለደ ተበተነ፤ ቅማንት ግን እንዳለ አለ፣ አገው፣ አርጎባ፣ ሞረት፣ ብሌን፣ ከይላ (ፈላሻ) አሉ፡፡ ጋፋት አሁን ጠፍቷል፤ በቆዳ መፋቅ ነበር የሚተዳደሩት፡፡ ሞረት ደግሞ ሸማና  የእጅ ጥበብ ሰሪ ናቸው፤ ሰሜን ሸዋ ውስጥ ይኖራሉ፡፡ አርጎባ ደግሞ በተለያዩ ክልሎች ተበጣጥሶ የተቀመጠ ነው፡፡ አገውም ደቡብና ሰሜን አገው ተብሎ ተበታትኖ አለ፡፡ መሃል ላይ ያለው እንግዲህ ቅማንት ነው፡፡ ቅማንት ከዘረዘርናቸው ብሄሮች በቁጥር በብዛት ይበልጣል፡፡ በጎንደር ውስጥ በ4 ወረዳዎች ከሚሊዮን በላይ የሆኑ ቅማንቶች አሉ፡፡ ግን በጣም የታፈነ ብሄር ነው፡፡ እንዲታወቅ አይፈለግም፡፡ ከባድ ጫና አለብን፡፡
ለምንድነው እንዲታወቅ የማይፈለገው?
ለኛም ሚስጢር ሆኖብናል፡፡ ወደፊት ይህን ሚስጢር እናወጣው ይሆናል፡፡ አሁን እያጠናነው ነው፡፡ የክልሉ መንግስት ለኛ እውቅና ለመስጠት የሞት ያህል ነው የሆነበት፣ ለምን እንደሆነ አይገባንም፡፡ በታሪክ ሂደት እየቀነሰ መጣ እንጂ ይህ ብሄር ከቀደምት የአፍሪካ ብሎም የኢትዮጵያ ዘሮች  የፖለቲካና ማህበራዊ ስፋት የነበረው ብሄር ነው፡፡ እኛ ቅማንትን ስንገልፅ ከመጀመሪያው የዘር መነሻ ጀምረን ነው፡፡ አማራዎች የዘር መነሻችሁን ግለፁ ብንላቸው የዘር መነሻ የላቸውም፡፡ አማራነት የተስፋፋው ከክርስትና ሃይማኖት መስፋፋት ጋር ተያይዞ ነው፡፡ የተጠመቀ አማራ ተባለ፡፡ አገው፣ ቅማንቱ፣ ከይላው ወዘተ ሲጠመቅ አማራ ተባለ እንጂ እገሌ፣ እገሌን ወለደ እያልክ የአማራን የዘር መነሻ አታስቀምጠውም፡፡ ይሄ ችግር ስላለ ቅማንት ስሙ እንዳይነሳ ይፈለጋል፡፡
እኛ ስለ ጎንደር፣ ስለፋሲል ግንብ የሚወራውን ሁሉ በሬዲዮ እየሰማን ከመሳቅ ውጪ በአሁን ሰዓት ምንም ማለት አንችልም፡፡ ስለፋሲልና ስለጎንደር መናገር የሚችለው ቅማንት ብቻ ነበር፡፡ ሌላ ማንም ሊናገር አይችልም ነበር፡፡ ግን ማንም ተነስቶ ሲዋሽ ስታየው ደምህን ያፈላዋል፡፡ የጎንደር ነገስታት የቅማንት ብሄር አባላት ናቸው ነው የሚሉት?
 ባይሆንም ስለታሪኩ መናገር የሚችለው ቅማንት ነው፡፡ እርግጥ እነዚህ ነገስታት ከሸዋ ተሰደው የመጡ ናቸው፡፡ በዚያ ሰዓት ደግሞ ሸዋም ቢሆን ቅማንት ነው የነበረው፡፡ ነገር ግን አስቀድሞ ወደ ክርስትና የተለወጠ በመሆኑ፣ ቅማንትነትን እየተወ አማራ ተባለ፡፡ እነዚህ ሰዎች ወደ ጎንደር ለመግባት ሲሞክሩ፣ ቅማንት አላስገባ ብሏቸው 70 ዓመት ፈጅቶባቸዋል፡፡ በኋላ ነው በስንት መከራ የገቡት፡፡
ቅማንት እንግዲህ የሰሜን ኢትዮጵያን ከፈጠሩት አንዱ ነው፡፡ ከከነአን ቅማንት ሲወጣ፣ ከኩሽ ደግሞ የኦሮሞ ብሄርን እናወጣለን፡፡ ለእኛ ወንድሞቻችን ናቸው፡፡ ምዝራይብ የሚባለው ደግሞ መነሻው ካይሮ ነች፡፡ ጥንት ምስር ተብላ ትጠራለች፡፡ በዚያ አካባቢ ያሉት ህዝቦች የምዝራይብ ዘሮች ናቸው፡፡ አሁን የቀሩት ጥቂት ናቸው፡፡ በአልጄሪያ የ“በርበር” ህዝቦች የሚባሉት ማለት ነው፡፡ የ“ፋጥ” ደግሞ ፍልስጤማውያን ናቸው፡፡ አረቦች ከፐርሺያ፣ ከኢንዶኔዢያና ከሩቅ ምስራቅ የመጡ ህዝቦች ናቸው፡፡ የአረብ ምድር የኛ ነው፤ ሰዎቹ የመጀመሪያዎቹን ሰዎች አጥፍተው ኖሩበት እንጂ የእነሱ አይደለም፡፡ በቅማንትኛ “አረቢያ” ማለት የእህል ምድር ማለት ነው፡፡ ከውሃ ጥፋት በኋላ ሰምጦ ምድረ በዳ ይሁን እንጂ ከዚያ በፊት የበግ፣ የፈረስ፣ የእህል ምድር ነው፡፡
የቅማንት ሃይማኖት ምንድን ነው?
አሁን ከብሄረሰቡ 98 በመቶ የሚሆነው የተለያዩ የክርስትና እምነቶች ተከታይ ነው፡፡ ሙስሊምም አለ፡፡ የቀድሞውን ህገ ልቦናም የሚከተሉ አሉ፡፡ የእነ አብርሃም ሃይማኖት የሆነው ህገ ልቦና የቅማንቶች ቀዳሚ እምነት ነው፡፡ የህገ ልቦናው መሰረቶች የሆኑትን 5 መመሪያዎች ይከተላሉ፡፡
5ቱ መመሪያዎች ምንድን ናቸው?
በአይሁድ እምነት ካሉት 10 ትዕዛዛት 5 ያህሉ ማለት ነው፡፡ ሙሉ ለሙሉ ባላስታውሳቸውም አትስረቅ፣ አትግደል፣ አታመንዝር ወዘተ የሚባሉት ናቸው፡፡ ቄሶች አሉ፣ በጫካ ውስጥ ሆነው የአብርሃምን ቅዳሴ ይቀድሳሉ፡፡
ለቅማንት ብሄር መዳከም ምክንያቱ ምንድን ነው?
በሌላው የሚደርስበት ጫና ነው፡፡ በተለይም የክርስትና እምነት መስፋፋት፡፡ ክርስትና በአክሱም በኩል መጣ፣ ያመነ የተጠመቀ ይድናል የሚለው ታወጀ፡፡ ቅማንቶች ደግሞ “አባሽቲ ሸምዲ ደደብቲ” አሉ “ባባትህ እደር በሸማህ ተቀበር” ማለት ነው። በአዲስ መጤ ሃይማኖት አትታለል ማለት ነው። በዚህ የተነሳ በአክሱምና በአካባቢው መኖር የሚችሉት የተጠመቁ ብቻ ናቸው፤ ያልተጠመቁ ተከዜን ተሻግረው ወዲያ ማዶ ይሂዱ ተባለ፡፡ በዚያው ከተከዜ ወደዚህ በሶስት አቅጣጫ ፍልሰት ሆነ፡፡ አንደኛው አቅጣጫ በዋግ በኩል ነው፡፡ ዋግ የደረሱ የቅማንት አባቶች “ዋያ አክሱም ከውጋላትን ነው” አሉ፤ ይህ ማለት አክሱምን የሚመስል ሃገር አግኝተናል ማለት ነው፡፡ ወደ ሰሜን አቅጣጫ የመጡት ደግሞ በብዛት የህገ ልቦናው የሃይማኖት መሪዎች ናቸው፡፡ ቦታው ሲደርሱ “ድቢ ሸልሚ ጋጋ ከውጋላትን ነው” አሉ። በተራራ የጨለመ ሃገር ውስጥ ገብተናል የሚል ትርጓሜ አለው፡፡ በወልቃይት በኩል የመጡት ደግሞ “ውላጋ ከውጋላትን ነው” አሉ፡፡ እኛ ሜዳ በሆነ ሃገር ውስጥ ገብተናል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የሰፈሩት ከሰሜን ተራራ አንስቶ እስከ ፓዌ ተራራ ነው፡፡ ወደ ተራራ የገፋቸውም ጦርነት ነው፡፡
ከኢትዮጵያ ውጪስ የቅማንት ዘር አለ?  
በኑቢያ ዘመነ መንግስት ቅማንት ሰፊ፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ ስሟ አራት ነው፡፡ የመጀመሪያው ኑቢያ፣ ቀጥሎ ኩሽ፣ ቀጥሎ አበሽ፣ ከዚያ ኢትዮጵያ ሆነ። በኑብያ ዘመን የቅማንት ግዛት እስከ ፐርሺያ፣ ምዕራብ ህንድ እና ሁሉንም አፍሪካ እና መካከለኛው ምስራቅን ያጠቃልል ነበር፡፡
መጀመሪያ የቅማንትን የማንነት ጥያቄ ይዤ የተነሳሁት እኔ ነኝ ብለዋል፡፡ ታሪኩን እንዴት ሊያውቁ ቻሉ? ጥናቶችስ አድርገዋል?
 የአባቴ አባት በጣም ነብይ ነበሩ፡፡ አንድ ምክር መከሩኝ፤ ይሄን ህዝብ የምታስጠራው አንተ ነህ፡፡ ጊዜው ሲደርስ ያለፍርሃት ለብሄረሰቡ መብት ታገል፣ ስሙን እንደገና አንሳው፤ ያኔ የኛ ህዝብ ቋንቋውን ያሳድጋል፤ ማንነቱ ይከበራል፤ እንደገና ቅማንትነት ይነግሳል አሉኝ፡፡ የሳቸውን ቃል ይዤ ተነሳሁ። በዚህም ብዙ መከራና ፈተና ገጥሞኛል፡፡ በፊት ጥቂት ሆነን እንታገል ነበር፤ ዛሬ ህዝቡ ሁሉ ሆ! ብሎ ተነስቶ እየታገለ ነው፡፡ መጀመሪያ ላይ ህዝቡ “ቅማንት ነኝ” ማለትን እንደ ሃፍረት ይቆጥረው ነበር። የቅማንት ብሄረሰብ የልማት ማህበርን በ1984 መሰረትኩ። በዚያ ማህበር ስም እየዞርኩ “እኔ ቅማንት ነኝ” እያላችሁ ራሳችሁን ግለፁ፡፡ ህገ መንግስቱ ለኛ መጥቷል፤ ተጠቃሚ መሆን አለብን” እያልኩ ከሃገር ሃገር በእግሬ እየዞርኩ አስተማርኩ፡፡ እግረ መንገዴንም “የቅማንት ህዝብ ታሪክ” የምትል ትንሽ መፅሐፍ ፃፍኩ፡፡ እሷ ከወጣች በኋላ በብሄረሰቡ ዙሪያ ውይይቱ ተስፋፋ፡፡ መፅሃፏ ትኩሳት አጫረች። በዚህ የተነሳ ብዙ መከራ ደርሶብኛል፡፡
አሁን ታዲያ ምን ውጤት አገኛችሁ?
ከክልሉ መንግስት እና ከፊውዳሉ ጋር የነበረው ትግል ቀላል አልነበረም፡፡ ቅማንት አይደለንም ስንል ኖረን እንዴት ቅማንት ነን  እንላለን የሚል ሃፍረት ያደረባቸው፣ ያንን የስነ ልቦና ዝቅጠት ለማላቀቅ ብዙ ጊዜ ፈጅቷል፡፡ አሁን አማራውም ከኛ ጋ ነው፡፡ ለኛ የሚወግኑ አማራዎች፤ አገው የብሄርነት እውቅና ካገኘ ቅማንት ለምን አያገኝም ብለው ራሳቸው ጥያቄውን እየደገፉ ነው፡፡ ቅማንቱም “በቅማንትነቴ እኮራለሁ” እያለ ዛሬ በግልፅ እየተናገረ ነው፡፡ አመለካከቱ ተለውጧል፡፡
የቋንቋው ት/ቤቶችን በየቀበሌው ቤት ተከራይተን በመክፈት ማስተማሩን ተያይዘነዋል፡፡ የመንግስት ት/ቤትማ ማን አድርሶን፡፡ መንግስት እኮ እንደ ተቃዋሚ ነው የሚቆጥረን፡፡ እኔ በዚህ በጣም አፍሬያለሁ፡፡ በዚህ መልኩ አንዳንዶች ትግላችንን እያሰናከሉ፣ እስከዛሬ ቢያቆዩትም እግዚሃር ይመስገን አሁን እያለቀ ነው፤ እየተሳካም ነው፡፡
ኦሮሞውና ቅማንቱ አልተቀላቀለም? በአንድ ወቅት ኦሮሞዎች የሰሜን ኢትዮጵያን እስከማስተዳደር ደርሰው ነበር ብዬ ነው ጥያቄውን ያነሳሁት…
ኦሮሞው፣ አገው እና ቅማንት የተቀራረቡ ህዝቦች ናቸው፡፡ ሜሮይ ላይ የሃማቲክ ህዝቦች የምንላቸው አገው፣ ቅማንት የመሳሰሉት ናቸው። የኩሸቲክ ህዝቦች የሜሮይ ስልጣኔ ሲወድቅ ካርቱምን የተቆጣጠሩ ናቸው፡፡ ከኦሮሞ፣ ከአገው፣ ከቅማንትና ከሌሎችም ህዝቦች የተውጣጣ ነው። በክርስትና የተነሳ ህዝቡ በሙሉ አንድ ብሄር ሆኖ አማራ ተባለ። ኦሮሞውም በዚህ ሂደት አማራ ሆኗል፡፡ ቅማንት እንደውም የአማርኛ ቋንቋ ከኔ ላይ ነው ያደገው፣ የራሴ ቋንቋ ነው ብሎ ያምናል፡፡
አማርኛ ቋንቋ በጣም የጠራውና በእግሩ የቆመው ጎንደር ላይ ነው፡፡ የይኩኖ አምላክንም፣ የነአኩቶ ለአብንም አማርኛ አይተነዋል፤ የተሰባበረ አማርኛ ነበር፡፡ ነገር ግን አማርኛ በእግሩ የቆመው ጎንደር ላይ በቅማንት ህዝብ ጀርባ ላይ ነው፡፡ ስለዚህ ቅማንት ለኢትዮጵያ ቅርስ ነው፡፡ ቅማንትን ማጥፋት ማለት ትልቅ ቅርስ ማጥፋት ማለት ነው። ነገ ቅማንት ራሱን ሲያስተዳድር ጉዱ ይታያል፡፡ የታፈኑ እውነቶች ይወጣሉ፡፡
ቅማንቶችን በመልክ እና በቁመና አይተን ከሌላው ልንለያቸው እንችላለን? በባህል ረገድስ?
የቀድሞው ቅማንት የዛሬ አማራ የዛሬ፣ ትግሬ ብለን ነው የምንወስደው፡፡ ባህሉም ሁሉ የቅማንት ነው፡፡ የጎንደር ዘፈንና እስክስታ የቅማንት ነው። የነይርጋ ዱባለ ዘፈንና ዜማ የቅማንት ነው፣ ግን ሲዘፍኑ የቅማንትን ምድር ጎጡን አይጠሩትም፡፡ እሚጠሩት ቅማንት የሌለበትን ቦታ ነው፡፡ ትግሬ፣ አማራ፣ ቅማንት ነው፡፡ ባላገር ሄደህ ብታየው ምንም ልትለየው አትችልም፡፡ ምክንያቱም የዛሬ ማንነቱን የያዘው በእምነት ነው፡፡ ክርስትናን በመቀበሉ እንጂ በደም አልተለወጠም፡፡
ጎንደር የሚለው ቃል ትርጉሙ ምንድንነው?    
የጌታ መነሻ ማለት ነው፡፡
የጌታ መነሻ ማለት?
እንግዲህ አንዱን የውሸት ታሪክ ትንሽ ልምዘዝልህ ማለት ነው፡፡ ከውሃ ጥፋት በኋላ አባታችን ኖህ፤ መርከብ ሰርቶ በመርከብ ነው ቤተሰቡ የተጠለሉት፤ መርከቧ ተንሳፋ አራራት ተራራ ላይ ተሰቀለች፡፡ ውሃው ሲጎድል ወጥተው ሲያዩ፣ መውረጃ የሌለው ተራራ ላይ ነው የተሰቀሉት፡፡ በዚህን ጊዜ ያለቅሳሉ፣ እግዚአብሔር በቅርበት ከሳቸው ጋር ስለነበር “አታልቅስ መውረጃ ተሰርቶልሃል፤ ሂድ ወደ አባትህ ሃገር ወደ ጊዮን” ይላቸዋል፡፡ ጊዮን ማለት ጣና እና አባይ ነው፡፡ መጡ፡፡ የተቀመጡበት ቦታዎች ሁሉ አሉ፡፡ ለወደፊት እናወጣቸዋለን፣ ህዝብ እንዲያውቀው ይደረጋል፡፡ የጥንቱ የቅማንት ታሪክ እንዲህ ነበር፤ ዛሬ ደግሞ እንዲህ ሆነ ተብሎ መቅረብ ነበረበት፡፡
ወደ ኖህ ታሪክ ልመልስህና እሳቸው እዚሁ ኖሩ፡፡ ልጆቻቸው ግማሾቹ ወደ ኤሽያ ሄዱ፣ ካም በአፍሪካ ምድር ተበተነ፡፡ እሳቸው ጎንደር መጥተው ኖረው፣ ሞቱ፣ እዚሁ ተቀበሩ፡፡ መቃብራቸው ላይ ትልቅ ቤተ መንግስት ተተከለ፣ ያ ቤተመንግስት ዛሬ የፋሲል ግንብ እያለ ቱሪስቱ የሚጎበኘው ነው፡፡ ከስሩ የሳቸው አፅም ነው ያለበት፡፡ አፄ ፋሲል ቤተ-መንግስቱን ከመትከላቸው በፊት በቅማንቶች ህገ ልቦና እምነት ይቀደስበት ነበር፡፡ ሲቀድሱ በዜማው መሃል “ጎሃይደር” ይላሉ፤ ትርጉሙ “ጌታው ቢነሱ” የሚል ነው፡፡ ጎንደር የሚለው ስም ከዚህ የመጣ እንጂ እንደሚባለው “ከተራራው ጎን እደር .. በዚያ እደር” የሚለው አይደለም፡፡ ከትግራይም የመጡ ሰዎች “ወይኒሰይኒ” የሚባሉ ህዝቦች ናቸው፡፡ ነገሩ “አፍ ያለሽ ያግባሽ ወይስ ከብት ያለሽ” ነው፡፡ በወቅቱ ቅማንት አፍ የለውም፤ መስማት ብቻ ነበር ያለው እድል፡፡ እና ታሪክ ሁሉ ተዘበራርቆ ያስቅሃል… እኔ አንዳንዴ አምርሬ አለቅሳለሁ፡፡ በሚሊኒየሙ ጊዜ አንድ የቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ስለ ጎንደር ነግሬው፣ ሙሉ በሙሉ በኔ ስም ሌላ ታሪክ ነው ያወጣው። ይህን ትክክለኛውን ለእናንተ የነገርኩትን ታሪክ አይደለም ያቀረበው፡፡
የጥንቱ ቅማንት በምን ነበር የሚተዳደረው?
በእርሻ ነው፡፡ የእህል ምግብ፣ የእንስሳት ምግብ፤ ይሄን ብሉ፤ ያንን አትብሉ… ተብሎ የተመረጠው በቅማንቶች አይደለም እንዴ? ዋናው የቅማንት ታሪክ እኮ የነበረው አዲግራት ላይ ነው፡፡ ትግሬ ማለት በቅማንትኛ “ሰው ሳይመጣ” ማለት ነው። ከዚያ ደግሞ እንደርታ ተባለ፤ “ሰው መጣ” ማለት ነው፡፡ “አጋመ” ቅማንትኛ ነው፤ “የኛ ያልሆነ” ማለት ነው፡፡ ግዕዝ ቋንቋን ተቀበል ሲባል “የኛ ያልሆነን አንቀበልም” ብሎ በመቃወሙ የተሰጠ ስያሜ ነው። “ይርትላ” ኤርትራ ነው፤ “ሰው አልመጣም” ማለት ነው፡፡ እነ ሙሴ ባህረ ኤርትራን ሲያቋርጡ፣ እነሱን የተከተሉት በባህር ውስጥ ሰጥመው ቀሩ፤ ዞረው ሲያዩ ሰው አልመጣምና በዚያው “ሰው አልመጣም” ብለው ሰየሙት፡፡ እንግዲህ ኤርትራም ሆነ ትግሬ ቅማንት ነው ማለት ነው፡፡
ትግሬ የሚለው ቃል ከምን እንደመጣ ብዙ ፀሃፍትና የታሪክ ተመራማሪዎች ለማወቅ ጥረዋል፤ አልተሳካላቸውም፡፡ እውነቴን ነው የምልህ በንፁህ ልቦና ለሚያጠናው በቅማንት ውስጥ ተዝቆ የማያልቅ ታሪክ ነው ያለው፡፡
ይሄ ትውልድ ቅማንትን አላወቀውም፡፡ በ1987 ይሁን… በእርግጠኝነት አላስታውሰውም፡፡ አልማዝ መኮ የምትባል አፈጉባኤ ለሶስት ሰአት ቢሮዋ ስታነጋግረኝ፣ ቅዳሴዎቹን ሁሉ አስደምጫት ነበር። እሷም “ቅማንት ሲባል ተማሪ እያለሁ እሰማለሁ፤ እንዲህ ያለ ነገር ግን አይመስለኝም ነበር” አለችና “ግን የአማራው መንግስት እውቅናውን የሚሰጣችሁ አይመስለኝም፤ ያለፉሃል አለችኝ፡፡ እንዴት አድርገህ እንደምታልፈው አላውቅም፤ እኔ ዛሬውኑ ቢሰጥህ ደስ ይለኛል፤ የክልልህ መንግስት ግን አስቸጋሪ ነው” አለችኝ፡፡ እሷም መሯት ስለነበር  በዚያው ሄደች፡፡
ግራሃም ሃንኰክ ደግሞ በ“Sign and the Seal” መፅሃፉ የቅማንት ጉዳይ ሚስጥር ነው ብሎታል። እውነት እልሃለሁ ቅማንት ብዙ መከራን የተቀበለ የኢትዮጵያ ሚስጢር ነው፡፡ ደቡብ ኢትዮጵያም ስትሄድ እኮ ከዚሁ የሄዱ ናቸው፡፡ ለነሱ ማስታወሻ ጎንደር ላይ የሚደረግ ነገር አለ፡፡ ቡናን ሶስት ጊዜ እንጠጣዋለን፤ አባ አቦል፣ አባ በረካ፣ አባቶና ብለን እንጠጣዋለን፡፡ እነዚህ ሰዎች ናቸው ወደ ደቡብ ሄደው አባት ሆነው ብሄሮቹን የመሰረቱት፡፡
አባ አቦል ወደ ምዕራባዊ ደቡብ ሱዳንን ይዞ ወደታች ያለው ነው፤ አባቶና ደግሞ መካከለኛው ደቡብ ያሉትን መሰረቱ፡፡ አባ በረካ ከባሌ ጀምሮ እስከ ህንድ ውቅያኖስ ይደርሳል፡፡ ወሎ ላይ ስትሄድ ሶስት አባቶች አሉ፡፡ ወረባቡ፣ ወረይመኑ፣ ወረ ሸኩ ተብለው ይጠራሉ፡፡ የባቡ ልጆች፣ የይመኑ ልጆች፣ የሸኩ ልጆች ማለት ነው በቅማንትኛ፡፡ ወደ ጎጃም ስትሄድ ከዚህ ከኛ የሄዱት አንከሻ፣ ባንጫ፣ ኳኩራ፣ አዘና፣ ሜቲክሊ ናቸው፡፡
እዚህ የቀሩት ክድስቲ እና ክብሩ ናቸው፡፡ ክቡር፣ ክብርት እያልን የምንጠራራበት፣ ቤተክርስቲያን ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ የምንለው የኛ አባቶች ስያሜ ነው፡፡ ለሰሜን ኢትዮጵያ ሙሉ ታሪክ የሚሰጠው የኛ ታሪክ ብቻ ነው፡፡ ይሄን በትክክል የሚቃረን አልተገኘም፡፡
ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያቀረባችሁት ጥያቄ ምላሽ ካገኘ፣ የራሳችሁን አስተዳደር ትመሰርታላችሁ ማለት ነው?
አዎ! እንደሁኔታው የራሳችን አስተዳደር እንዲኖረን እንታገላለን፡፡ እኛም ኖርንበት አማራውም ኖረበት የሚጠቀመው ክልሉ ነው፡፡ በ2007 ዓ.ም ቅማንት ራሱን ያስተዳድራል ብለን እናምናለን። በህገ-መንግስቱ መሰረትም በፌደራል መንግስት የራሱ ወኪል ይኖሩታል ተብሎ ይታሰባል፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምላሽ እንዴት ነው?
ያገኘነው መልስ በድጋሚ ይጠና የሚል ነው። በጥናት ከሄድክ በኢትዮጵያ እንደቅማንት የተጠና የለም፡፡ ክልሉ ራሱ ሶስት ጊዜ አጥንቷል፣ እኛም ሁለት ጊዜ አጥንተን ሰጥተናል፤ አልቀበል እያሉ እንጂ፡፡ የመጨረሻ ጊዜ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አጥንቶ ሄዷል፤ ለውሳኔ ሲያቀርብ ምን እንደገጠመው አናውቅም፤ በድጋሚ መጠናት ያስፈልጋል ነው ያለው፡፡ በኛ በኩል እንኳን በድጋሚ እየደጋገመም ያጥና፤ ቅማንት ቅማንት ነው፡፡ ወጣቱም በሚገባ ቅማንትነቱን አውቋል፤ ጥያቄውንም እያነሳ ነው። እንደውም ባለፈው ብዙዎችን አስረውብን ነበር። ጥያቄውን ነገ ከነገ ወዲያ እያሉ ማሸት ተገቢ አይደለም፤ ቢለቁን ይሻላቸዋል፡፡       

የ”ዋቢ የግል ፕሬስ አሳታሚዎች የዘርፍ ማኅበር በኢትዮጵያ” መግለጫ


መሰባሰብ ከጀመረ ሁለት ዓመት የሆነውና ሕጋዊ ዕውቅና በሚያዝያ 30 ቀን 2006 ዓ.ም. ያገኘው “ዋቢ የግል ፕሬስ አሳታሚዎች የዘርፍ ማኅበር በኢትዮጵያ” በተደጋጋሚ ስብሰባዎቹ ከሕዝቡና ከደንበኞቹ ለአባል ጋዜጦችና መጽሔቶች የሚቀርቡትን ሐሳቦች አስተያየቶችና ቅሬታዎች ሲመረምርና ሲወያይበት ሰንብቷል፡፡ በዚህ ሳምንት ስብሰባውም ለአንባቢዎች መልስ ለመስጠት ይህን መግለጫ አውጥቷል፡፡
ከሚጻፈው ሐሳብ ጋር ይስማማ አይስማማ ሌላ ነገር ሆኖ በጋራ አንባቢው ኅብረተሰብ የሚያቀርበው ቅሬታ አለ፡፡ ቅሬታውም “ምነው በወቅቱ አትወጡም?”፣ ምነው ጊዜ ያለፈበት ወሬ ትሰጡናላችሁ፣ ምነው ጠቆረ፣ ምነው ባለ ቀለም የነበረው ጠፋ፣ ምነው ተዳከማችሁ፣ ምነው ጊዜ ያለፈበት የሥራና የጨረታ ማስታወቂያ ታስነብቡናላችሁ ወዘተ. ይላል፡፡
ከጋዜጣና ከመጽሔቶች ጋር በማስታወቂያና በስፖንሰርሺፕ የሚገናኝ አካልም ማስታወቂያችን በወቅቱ አልወጣም፣ ጊዜ አልፎበታል፣ ጭራሽ ባለቀለም የነበረው ጥቁርና ነጭ ሆኗል፣ ጭራሽ ቀለሙ ጠቁሮና ደብዝዞ አይታይም አይነበብም ለመክፈል እንቸገራለን ይላል፡፡
“ዋቢ የግል ፕሬስ አሳታሚዎች የዘርፍ ማኅበር በኢትዮጵያ” በማኅበሩ ተደጋጋሚ ስብሰባ እነዚህን በዝርዝርና በጥልቀት ተወያይቶ የሕዝብ ቅሬታና የደንቦች አቤቱታ እውነት እንደሆነ ተቀብሏል፤ አምኗል፡፡ ችግሩ ምን ላይ እንደሆነም ለሕዝብ ግልጽ ለማድረግ ይፈልጋል፡፡
በተከታታይና በተለያዩ መንገዶች በፕሬስ ሕትመቶች ላይ እየታየ ያለው ችግር በዋነኛነት ከማተሚያ ቤት ጋር የተየያዘ ነው፡፡ አብዛኛዎቻችን በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት እናሳትማለን። አንዳንዶቻችን በሌሎች ማተሚያ ቤቶች እናሳትማለን።
በተደጋጋሚ የሚታየው የማተሚያ ቤት ችግር አንዱ የሕትመት ማሽን ተበላሸ እየተባለ ጋዜጦችና መጽሔቶች በወቅቱ እንዳይወጡ መደረጉ ነው፡፡ የፈተና ወረቀት እየታተመ ስለሆነ ጋዜጣና መጽሔት በወቅቱ አይታተምም የሚልም ሌላው ምክንያት ነው፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች የፕሬስ ውጤቶች ቅዳሜና እሑድ መውጣት ያለባቸው ረቡዕና ሐሙስ ሲወጡ ይታያል፡፡ ይህ ሁኔታ የፕሬስ ቢዝነሱን በእጅጉ እየጐዳ ነው፡፡
ሌላው ችግር ገፅ ቀንሱ ወረቀት የለም ቀለም የለም የሚል ነው፡፡ ይህም ጋዜጦችና መጽሔቶች አንባቢዎች ከሚፈልጉትና ደንበኞች ከተዋዋሉት ጋር የሚሄድ ቁጥር እንዳያገኝ እያደረገና ሰውን እየጐዳ ነው፡፡
ቀለም የለም፣ ፕሌት የለም እየተባለ መልካችሁንና ይዘታችሁን ቀይሩ የሚል ጫናም ከማተሚያ ቤቶች እየመጣ ነው፡፡ ይህም በእጅጉ ቢዝነሱን እየጐዳ ነው፡፡
በተለይ በተለይ ደግሞ ደንበኞችን አክብሮና ተወያይቶ አወያይቶ የገበያ ዋጋን ከመወሰን ይልቅ በድንገት ዋጋ ተጨምሯል እያሉ ከፍተኛ የገንዘብ ኪሣራና ጫና መፍጠር በእጅጉ አስጊና አሳሳቢ ሁኔታ ሆኗል፡፡ የጥራት ጉድለትና ጋዜጦችና፣ መጽሔት ፎቶዎቻቸውና ጽሑፎቻቸው መነበብ በማይችሉበት ሁኔታ ተጨማልቆ መውጣትም ሌላው አስፈሪና አሳፋሪ፣ ቢዝነስን በእጅጉ እየጐዳ ያለ ተግባር ሆኗል፡፡
የተከበረው አንባቢ ኅብረተሰብና የቢዝነስ አጋራችን የሆነው አካል ችግራችን ከላይ እንደተጠቀሰው ከአቅማችን በላይ መሆኑን እንዲገነዘብልን በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡ የምንጠቀምበት ማተሚያ ቤት የራሱ የፕሬሱ አይደለምና ‹‹ዋቢ የግል ፕሬስ አሳታሚዎች የዘርፍ ማኅበር በኢትዮጵያ›› የማተሚያ ቤትን ችግር የራሱ ማተሚያ ቤት በማቋቋም ለመፍታት እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ሆኖም ግን ይህም በአጭር ጊዜ እውን ለማድረግ ቀላል ስለማይሆን ይህ መፍትሔ እስኪገኝ ድረስ ከመንግሥት ጋር ሆኖ ብርሃንና ሰላምና ሌሎች ማተሚያ ቤቶች የሚፈጥሩትን ችግር ለመፍታት ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው፡፡
በቅርብም ችግሩን በጋራ ዓይተንና ተወያይተን በጋራ መፍትሔ ለማስቀመጥ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝን ለማነጋገር በሚመለከተው አካል በኩል የቀጠሮ ቀን ጥያቄ አቅርበናል፡፡
እኛም የማኅበሩ አባላት የፕሬሶችን ችግር ለመፍታት ራሳችን ማድረግ የሚገባንን ሁሉ ለማድረግና ድክመቶቻችንንም፣ ችግሮቻችንንም አስወግደን በመጠናከር የሚገባንን ሁሉ ለማድረግ ተነስተናል፡፡ ከመንግሥት ጋር ሆነን ችግሩን ለመፍታትም መንግሥትን ጠይቀናል፡፡
ይህ እንዲህ ሆኖ ሕዝብም ዋነኛውና ወሳኙ አካል ስለሆነና የቆምንለት ዓላማ ተገቢ መረጃ ለሕዝብ በወቅቱና በጥራት መስጠትና ሕዝብን ማገልገል ስለሆነ ሕዝብም ችግራችንን ተረድቶ ይበልጥ የምናገለግልበትን አቅም እንድንገነባ በትዕግስት ከጐናችን እንዲቆም እንጠይቃለን፡፡
ዋቢ የግል ፕሬስ አሳታሚዎች የዘርፍ ማኅበር በኢትዮጵያ
            ሐምሌ 11 ቀን 2006 ዓ.ም.          

(ኣፀቢቕና ኣይንበኣስ፣ እንተ ተዓረቕና ከይንጠዓስ)

አንድ የአሜሪካ ጋዜጣ ላይ የሚከተለው ሰፍሯል፡፡ የሚከተለው ኩባንያ (መሥሪያ ቤት) አባል መሆን ይፈልጋሉ?” በሚል ርዕስ፡፡ ነገሩ ዕውነት ነው፡፡ ግን ላታምኑ ትችላላችሁ፡፡
ይህ ኩባንያ ከ500 ጥቂት ከፍ ያሉ ሠራተኞች አሉት፡፡
ኩባንያው የሚከተለው ስታቲስቲክስ አለው፡-
ካሉት አባላት 29ኙ በሚስቶቻቸው ላይ ግፍ በመፈፀም ተከሰዋል፡፡
7ቱ በማጭበርበር ወንጀል ተከሰው ታስረው ነበር፡፡
19ኙ የተሳሳተ ቼክ በፈረም ተከሰዋል፡፡
117ቱ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሁለት የንግድ ተቋማትን ኪሣራ ላይ ጥለዋል፡፡
3ቱ አስገድደው ደፍረዋል፡፡
71ዱ ከዚህ ቀደም ባደረሱት ጥፋት ክሬዲት ካርድ ማግኘት አይፈቀድላቸውም፡፡
14ቱ ከአንደዛዥ ዕፅ ጋር በተያያዘ ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡
8ቱ ከሱቅ ዕቃ ሲመነትፉ ተይዘው ታስረዋል፡፡
21ዱ በአሁኑ ጊዜ ክሳቸውን ለመከላከል ፍ/ቤት ይመላለሳሉ፡፡
ባለፈው ዓመት ብቻ 84ቱ ጠጥተውና ሰክረው በመንዳት ታስረዋል፡፡
እነዚህን ሁሉ ያቀፈው ይህ ድርጅት፤ የትኛው ይመስላችኋል?
ምናልባት የአሜሪካ ብሔራዊ ባንክ ነው ትሉ ይሆናል፡፡ ተሳስታችኋል (ሊሆን አይችልም ማለት ግን አይደለም)
አላወቃችሁም? ተስፋ ቆረጣችሁ?
መልሱ ምን መሰላችሁ?
535 አባላት ያሉት የዩናይትድ ስቴትስ ኮንግሬስ ነው፡፡
በየአመቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ህጐችን የሚያወጡትና ሁላችንንም ቀጥ - ለጥ ብላችሁ ተገዙ የሚሉን እነዚሁ የግብዝ ጥርቅሞች ናቸው፡፡
*   *   *
አመራሮች “የራስህን ዐይን ጉድፍ ሳታይ የሌላውን ጉድፍ ለማውጣት አትሞክር” የሚለውን፣ ራስን የማፅዳት መርህ የማወቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በሴቶች ላይ ያለን የበላይነት አባዜ ሳይወገድ፣ እጃችን ከማጭበርበር ወንጀል ሳይፀዳ፣ በየንግድ ተቋማቱ ውስጥ የተነካካንበትን ሁኔታ ሳናጠራ፤ ከተለያዩ ሱሶች የተገላገልን ሳንሆንና ከአልባሌ ወንጀሎች ክስ የራቀ የኋላ ታሪክ ሳይኖረን፤ ሌሎችን መምራት አዳጋች መሆኑ መቼም፤ ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ነው፡፡ በትምህርት ራስን ማብቃት ዋና ነገር ቢሆንም፤ በሥነ-ምግባራዊና ሥነ-ሰብዓዊ ክሂል ካልተደገፈ ጉዟችን ጎዶሎ ይሆንብናል፡፡
ዛሬ ሀገራችን የምትፈልጋቸው አያሌ ባለሙያዎች፣ በተለይ በአመራር ደረጃ ያሉቱ፤ ከትምህርታቸው በተጓዳኝ ልዩ ልዩ ንጥረ-ባህሪ ያላቸው ሊሆኑ ይገባል፡፡ ይህ ክሂል ከነዚህ ውስጥ የሚከተሉትን ያገናዘበ ቢሆን ይበጃል፡፡
ልዩነትን መወያየት የሚፈልግ ሰው ያስፈልጋል፡፡ (a bone to pick እንዲሉ)
መቼም ቢሆን ድብቅ ፍላጐት ያለው ሰው ጣጣ ነው፡፡ (an axe to grind እንዲሉ) ከዚያ ይሰውረን፣ የሚል ግልጽ ሰው ያሻናል፡፡
አንድ የተበላሸ ፍሬ ሙሉውን በርሜል ያበላሸዋል፡፡ አንድ ሞሳኝ ሰውም እንደዚያው ሁሉንም ሰው ያበላሻል፡፡
የተሳሳተው ዛፍ ላይ መጮህ (Barking up the wrong tree እንዲሉ) የተሳሳተ ጉዳይ ላይ ከተሳሳተ ሰው ጋር ማውራት ጅልነት መሆኑን የተገነዘበ የፖለቲካ መሪ፤ ያሻናል፡፡
ፈረንጆቹ ወይ ህፃን ወይ አዋቂ አለመሆን አለመታደል ነው ይሉናል (Between hay and grass እንዲሉ) ይህንን ልብ ያለ የፖለቲካ ሰው ይስጠን፡፡
ታገስ (Hold your horses ነው ነገሩ) ትልቅ የህይወት መርህ ነው፡፡ ዕለት ሠርክ ትዕግስት የሚጠይቁ አያሌ ውጣ ውረዶች አሉ፡፡ እነዚያን ለመወጣት የሚችል ሰው ይባርክልን፡፡
ሁሉን ነገር (kit and caboodle እንዲሉ) አጠቃሎ የማየት አስተውሎት ያለው የበሰለ ተቃዋሚ ይሰጠን ዘንድ እንፀልይ፡፡
“ከፈረሱ አፍ ስማ” የሚለው መርህ የገባቸው ሰዎች ያስፈልጉናል፡፡ በወሬ፣ በሃሜት፣ በጥቆማ፣ በስማ - በለው ከሚወቅሱና ከሚከሱ ይገላግሉናልና፡፡
Iron in the fire ይላሉ ፈረንጆች፡፡ ሁሉ ቦታ ጥልቅ ማለት አይገባም፡፡ ሁኔታዎችን ከማባባስና የከፉ ከማድረግ በቀር ምንም የረባ ዕድገት አናመጣም - በየነደደበት በመዶል፡፡
You aint the only duck in the pond ይህ ማለት በቁም ትርጉሙ ስናየው ኩሬው ውስጥ ያለኸው ዳክዬ አንተ ብቻ አይደህም የሚል ሲሆን፤ አገሩ ሁሉ ስላንተ የሚያወራ እንዳይመስልህ ማለትም ነው፡፡
ከላይ የጠቀስናቸውን ያህል ጠባያት በአግባቡና በቅጡ ከተቀዳጀን፤ ለመጪው ምርጫ፣ ፋይዳ መኖር ለዕለት - ተዕለት ዲሞክራሲያዊ አሂዶአችን፣ መሳካት ለፍትሕ - ርትዕ ርሃባችን መወገድ፣ ለመልካም አስተዳደር ዕውነተኛ ገጽታችን መበልፀግ፣ ለእጅ አመላችንና ለዕምነት ክልስነታችን መወገድ መጠነኛ አስተዋጽኦ ያደርግልናል፡፡
 “በሀገራችን ምርጫ በመጣ ሰዓት መንግስት ደግ ይሆናል” የሚል ሐሜታ ሁሌ ይነገራል። መንግስትም ይሰማል፡፡ ህዝብም ያውቃል፡፡ ይህን ሁኔታ ለመለወጥ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በእርግጥም ዲሞክራሪያዊት ሂደት መሆኑን ማመን አለብን፡፡ ተለዋጭ ሁኔታን መቋቋም ያስፈልጋል፡፡
እነሆ ይሆኑናል፣ ይበጁናል፣ የምንላቸውን ሰዎች ስንመርጥ ሙያ - ከምግባር፣ ልብ -ከልቦና ያላቸው ቢሆን መልካም ነው፡፡ “አስወርተህ ሹመኝ፣ ዘርፌ አበላሃለሁ” የሚሊ መሆን የለባቸውም፡፡ ገዢ ፓርቲና ተገዢ ፓርቲ የጋራ የጨዋታ ሜዳ፣ የጋራ የጨዋታ ሕግ፣ ባላቸው አገር ደግሞ ሁነኛ ምርጫ ይኖራል ብሎ ማሰብ፣ ጤናማ ላገር ማሰብ ነው፡፡ አዎንታዊነት ነው! የሻከረው ሊላግ፣ የከረረው ሊላላ፣ የጎደጎደው ሊሞላ ይችል ዘንድ የሁሉም ቅን ልቦና ያስፈልጋል፡፡ እስከመቼ ተሸካክረን? እስከመቼ ተቆሳስለን? እስከመቼ ተወነጃጅለን? እርስ በርስም ሆነ፣ ጎራ ለይተንስ እስከመቼ ተጠላልፈን? እስከመቼስ ብቻዬን እሰራዋለሁ ብለን እንዘልቀዋለን፡፡ ዕውነት ለሀገር ብለን ከሆነ ደፋ ቀና የምንለው፣ ዕውነት ለህዝብ ብለን ከሆነ በፖለቲካ የምንሞራረደው፤ በጠላትነት መፈራረጅና ለመጠፋፋት የምንሽቀዳደምበት ሜዳ ምንጠራ ውስጥ መግባት የለብንም፡፡ የሄድነውን መንገድ ዘወር ብለን ስናይ በራሳችን ላይ መሳቃችን አይቀሬ ነው፡፡ ታሪካችን የጠብ ነው፡፡ የመጣላት ነው፡፡ ቢያንስ ምርጫዎች ሲደጋገሙ ከጠቡ ቀነስ እያደረጉልን፣ እያሰለጠኑን መሄድ አለባቸው፡፡ “በጣም አንጣላ፤ ከታረቅን እንዳይቆጨን” የሚለው የትግሪኛ ተረት ይህን ይነግረናል፡፡

Published in ርዕሰ አንቀፅ

በዚህ እትም ለንባብ ያበቃነው የሁለት እናቶችን የእርግዝና እና የወሊድ ገጠመኞች እና የህክምና ባለሙያዎችን አስተያየት ነው፡፡ አንዱዋ እናት ወ/ሮ ልእልና ይበልጣል ስትሆን ሌላዋ ደግሞ ወ/ሮ መቅደስ መሐሪ ናት፡፡ ወ/ሮ ልእልና እንደሰጠችው እማኝነት ልጁዋን የተገላገለችው በምጥ ሳይሆን በቀዶ ሕክምና ነው፡፡ ነገር ግን የህኪምዋም ሆነ የእርስዋ የመጀመሪያ ውሳኔ በምጥ እንደምትወልድ ነበር፡፡ እንደሚከተለው ሀሳቡዋን ትገልጻለች፡፡ “...እኔ የመተንፈሻ አካል ችግር ወይንም የብርድ አለርጂክ ስላለብኝ ወደ መውለጃዬ ቀን እየተቃረብኩ ስመጣ ምናልባት በምጥ መውለድ ያልቻልኩ እንደሆነ ወደ ኦፕራሲዮኑ መሄዴ ስለማይቀር ምን አይነት ማደንዘዣ ነው መውሰድ ያለብኝ በማለት ሐኪሜን ሳማክረው ሙሉ ማደንዘዣ ሳይሆን በጀርባ የሚሰጠውን ግማሽ መውሰድ እንዳለብኝ ነገረኝ፡፡ ይህንኑ ሀሳብ ይዤ ወደ ጽንስና ማህጸን ሐኪሙ ማለትም እኔን ሲከታተለኝ ወደነበረው ዶ/ር ሄድኩ፡፡ የሄድኩበት ዋና ምክንያትም እሱን ካነጋገርኩ በሁዋላ በተጨማሪም የሰመመን ሰጪዋን ለማነጋገር ነበር፡፡ ነገር ግን ምርመራው ሲደረግልኝ የስኩዋር መጠኔ ከፍ ብሎ ታየ፡፡ እንደገናም የልጄም የልብ ምት ጨምሮ ነበር፡፡ እኔም ባለቤቴም ተደናገጥን፡፡ ከዚያም ሐኪሙም በአስቸኳይ እንድተኛ እና እንድወልድ በማዘዙ ሳላስበው ምጡ ቀርቶ በኦፕራሲዮን እንድወልድ ተደረገ፡፡ ከቤተሰቦቼ እንደተነገረኝ ከሆነ ሐኪሙ ልክ እኔን አዋልዶ ሲወጣ... ...እንዴት ነች? እንዴት ነች?...ሲሉት “...እሱዋ ምን ትሆናለች... ወንድ ልጅ ተገላግላለች...እኔ ነኝ እንጂ... ይላል... በሁዋላም እናቴ... ውይ...አንተ ምን ሆንክ? ስትለው...ይህንን ጮማ ለማገናኘት (ለመስፋት) ስታገል ደከመኝ...አለ፡፡ እኔም ደግሞ ወደ አልጋዬ ተመልሼ ከሰመመኔ በደንብ ስነቃ... ቤተሰቦቼ ...እንዴት ነበር? ሲሉኝ... “...ሐኪሜ ብቻውን 50/ኪሎ ጤፍ በሆዴ ላይ እንደሚያቦካ አይነት ስሜት ይሰማኝ ነበር...” ብያለሁ፡፡ ዶ/ር ሰሎሞን ቁምቢ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በምጥ መውለድን በሚመለከት የሚከተለውን ብለዋል፡፡ “...በምጥ መውለድ ያማል፡፡ ምጥ እንደሚያም ማንም ያውቃል፡፡ አንድ መጽሐፍ... ምጥ ምን ያህል እንደሚያም ሲጠቅስ በድንገት ሰዎች የሚሞቱበት የልብ ሕመም ብቻ ሲበልጠው በስተቀረ አቻ የሌለው ሕመም ነው፡፡ ነገር ግን ሕመሙ እንደሚኖር ታውቆ እና የስነልቡና ዝግጅት ተደርጎበት እንዲሁም ከዚያ የሚገኘው ውጤት እንደሽልማት የሚያስደስት ስለሆነ ያንን ሕመም የሚያስረሳ ይሆናል እንጂ ሕመሙ ሕመም ነው፡፡ ነገር ግን ተፈጥሮአዊ ሂደት ስለሆነ ማንኛዋም ሴት ችግር ካልገጠማት በስተቀር በምጥ እንድትወልድ ነው የሚመከረው፡፡...” ወ/ሮ ልእልና እንዲህ ትላለች፡፡ “...በእድሜዬ ወደ ሰላሳው አመት የገባሁ ስለሆነ ድጋሚ ልጅ መውለድ ስለምፈልግ ኦፕራሲዮኑን አልፈልገውም ነበር፡፡ ምክንያቱም ማራራቅ በሚባለው ፕሮግራም ሶስትእና አራት አመት መቆየት ለእኔ ከእድሜዬም አንጻር ስለሚከብደኝ ነበር፡፡ ነገር ግን ምንም ማድረግ አልቻልኩም፡፡ ኪሎዬ ወደ 100/ደርሶ ነበር፡፡ ምግቤን በተለይም ወደ ስምንትና ከዚያ በሁዋላ ባለው ጊዜ ስኩዋር ቴምር የመሳሰሉትን በጣም እወስድ ነበር፡፡ የእርግዝና ስሜት እንጂ ሌላ ነገር ነው ብዬ አላሰብኩም ነበር፡፡ ነገር ግን በእራሴም ላይ የጤና ችግር አስከትሎ ልጄንም ላጣው ስለነበር ሐኪሜ ከእግዚአብሔር ጋር ከአደጋ አውጥቶኛል፡፡” ዶ/ር መብራቱ ጀምበር የጽንስና ማህጸን ሐኪም እና የብራስ የእናቶችና የህጸናት ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር እንደሚሉት እርግዝና በተቻለ መጠን ከ24-35 አመት እድሜ ክልል ውስጥ ቢሆን ይመረጣል፡፡ እስከ 24 የሚቆይበት ምክንያት ለትምህርቱ እና ለእድገቱ መመቻቸት ሲባል ሲሆን ከ35/ አመት በሁዋላ አለማርገዝ የሚመረጥበት ምክንያት ደግሞ ለተለያዩ ችግሮች መጋለጥን ለማስወገድ ሲባል ነው፡፡” የሁለተኛዋ አስተያየት ሰጪ ወ/ሮ መቅድስ መሐሪ ገጠመኝ የሚከተለው ነው፡፡ “...ባለቤቴ እና እኔ ልንጋባ ስንል ሳላስበው ድንገት ነው ያረገዝኩት፡፡ እርግዝና ለእኔ ቀላል አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ከመጠን በላይ ወፍሬ ነበረ፡፡ ባረገዝኩበት ወቅት እድሜዬ 23 አመት/ ሲሆን ሱሪ የምለብሰው 28 ቁጥር ነበር፡፡ በዚህ ላይ ልክ እንዳረገዝኩ ስራ ተቀጥሬ አገር ለውጬ ወደ ሞቃታማ አካባቢ ሄጄ ነበር፡፡ ምንም እንኩዋን ሕመም ባይሰማኝም ብቻዬን ስለነበርኩ ጭንቀት ይሰማኝ ነበር፡፡ ዙሪያዬን የነበሩ ሰዎችም በየጊዜው ክብደቴ እየጨመረ ሲሄድ ያስፈራሩኝ ነበር፡፡ ባረገዝኩበት ወቅት ወደ ሰላሳ ኪሎ ግራም ክብደት በመጨመሬ በጣም እፈራ ነበር፡፡ ከማርገዜ በፊት እስፖርት እሰራ ስለነበር እና በእርግዝናው ወቅት እስፖርቱን ስላቋረጥኩኝ ምናልባትም ክብደቴን ከልክ በላይ ያደረገው እሱ ይሆናል የሚል ጥርጣሬ አለኝ፡፡ ዶ/ር ሰሎሞን ቁምቢ እስፖርትን እና እርግዝናን በሚመለከት እንዲህ ብለዋል፡፡ “...አንዳንድ ሰዎች ተሳስተው ይሁን ወይንም ከልክ በላይ ጥንቃቄ ለማድረግ... ብቻ በራሳቸው ምክንያት በእርግዝና ወቅት እስፖርት ማድረግ አይመከርም ብለው ያስባሉ፡፡ ነገር ግን አዲስ አይነት እና ከበድ ያለ አይሁን እንጂ ቀደም ሲል የተለመደውን የአካል እንቅስቃሴ እንዲሁም ውሃ ዋና የመሳሰሉት በእርግዝና ጊዜ አይከለከሉም፡፡ ጠዋትም ይሁን ወደ አመሻሹ የእግር ጉዞ ማድረግ የሰውነት ማጎልመሻ እንቅስቃሴን ለእርጉዝ ሴት በሚያመች መልኩ መስራት ይመከራል፡፡ ነገር ግን እንደ ቦክስ ወይንም ከበድ ያለ የአካል እንቅስቃሴ የሚፈልግ እስፖርት ለመስራት ግን አስቸጋሪ እንደሚሆን አይጠረጠርም፡፡” ወ/ሮ መቅደስ አመጋገብዋን በተመለከተ የሚከተለውን ብላለች፡፡ “...ምግብን በመመገብ በኩል ምንም ችግር አልነበረብኝም፡፡ በጣም በተከታታይ ይርበኝ ስለነበር ሌሊት ሳይቀር እመገብ ነበር፡፡ የተለያዩ ምግቦችን በየሰአቱ ሳይቀር ከጠረጴዛዬ ላይ አመቻችቼ እወስድ ነበር፡፡ በተለይም ከሰባተኛው ወር በሁዋላ የነበረውን ሁኔታ ማስታወስ ይከብደኛል፡፡ እናም ከመውለዴ በፊት 68/ኪሎ የነበርኩት ልወልድ አካባቢ ወደ 95/ኪሎ ገባሁ፡፡ ከዚያም በድንጋጤ መመገቤን አቆምኩ ማለት እችላለሁ፡፡ በዚያ ምክንያትም ከእናቴ ጋር ጭቅጭቅ ሆነ፡፡ ውሀ መጠጣት፣ ቅጠላ ቅጠል መውሰድ ጀመርኩ፡፡ ግን በዚያች ወቅት ምንም እንኩዋን እንደፈራሁት መቶ ኪሎ/ባልገባም ወደታች ግን ምንም አልቀነስኩም፡፡ ወ/ሮ ልእልና አመጋገብን በተመለከተ የምታስታውሰው እንደሚከተለው ነው፡፡ “...እኔ በጣም የምወስደው ጣፋጭ ነገር ነበር፡፡ በእርግጥ ሌላ ነገር አልመገብም ማለት አይደለም፡፡ የደሜ አይነት ኦ ስለሆነና ስጋ አያወፍርም ብዬ ስለማስብ ስጋ ...ጮማ የሆነ ሁሉ እመገብ ነበር፡፡ ከዚያ ውጭ ግን ልክ እንደትንሽ ልጅ አይስክሬም አይቀረኝም ነበር፡፡ ባለቤቴ ይከፋታል ብሎ ስለሚያስብ ግዛልኝ ያልኩትን ነገር ሁሉ ገዝቶ ይገባል፡፡ ምግብ ሲቀርብ በእሱም እጅ በእራሴም እጅ ነበር የምመገበው፡፡ እንዲያውም አንድ ቀን እናቴ ይሄንን ታዝባ ...እባክህን ...አንተ ማጉረስህን ቀንስ እና በእራስዋ እጅ ትብላ፡፡ ወይንም ደግሞ በእራስዋ እጅ መብላትዋን ትተውና አንተ አጉርሳት ብላ ተናግራለች፡፡ ምክንያቱም ውፍረቴ እያደር ስለሚያሳስብ ነበር፡፡ በሁዋላም የልጄ የልብ ምት የመፍጠኑ ምክንያት ከዚህ ጋር ተያይዞ መሆኑን ባለሙያዎች ነግረውኛል፡፡ ወ/ሮ መቅደስ እንደምታስታውሰው ለመውለድ ወደሆስፒታል የገባች እለት የዋለችው ከቢሮዋ ነበር፡፡ “...ከቢሮዬ የምውልበት ምክንያት ከቤቴ እንዳልውል ብዬ ነበር፡፡ ምክንያቱም ከቤቴ ስውል ይርበኛል፡፡ ከራበኝ ደግሞ እበላለሁ፡፡ ነገር ግን የዚያን እለት የተወከልኩበት ኃላፊነት ስለነበረኝ ስብሰባ መምራት ይጠበቅብኝ ነበር፡፡ ነገር ግን በድንገት የሽርት ውሀ ፈሰሰኝ፡፡ ለእናቴ ስልክ ደውዬ ሁኔታውን ስነግራት በጣም ተቆጣችኝ፡፡ ውሀው ይፈሳል እንጂ እኔ እኮ ደህና ነኝ... ስላት በይ አሁኑኑ ስብሰባ ሳትገቢ ለሐኪምሽ ደውይና መልሱን ንገሪኝ አለችኝ፡፡ ደነገጥኩና ለሐኪሜ ስደውልለት በይ ባስቸኳይ ነይ አለኝ፡፡ ...በቃ... ስብሰባውን ትቼ...ወደ ሆስፒታል ሄድኩ... ልጁም ኪሎው ከባድ ስለነበር በሲዘር..ኦፕራሲዮን.. ወለድኩ፡፡” ወ/ሮ ልእልና ይበልጣል እና ወ/ሮ መቅደስ መሐሪ በተለያዩ የግል ሆስፒታሎች የወለዱ ሲሆን ሁለቱም ተመሳሳይ ቅሬታዎች አሉዋቸው፡፡ በእርግዝና ወቅት በተለይም ለመውለድ በሚዳረሱበት ጊዜ የጡትን ጫፍ እንዴት ማውጣት እንደሚገባ ...እንዴት ልጅን ማጥባት እንዳለባት አንዲት እናት ተገቢውን ልምምድ የሚያደርጉባቸው ተቋማት የመኖራቸውን ያህል አንዳንዶቹ ደግሞ ጭርሱንም አይሞክሩትም፡፡ አንዲት እናት ያውም በኦፕራሲዮን ወልዳ ሕመሙ...መድሀኒቱ አድክሞአት ባለችበት ሁኔታ እንኩዋንስ ልጅዋን ልታጠባ አካልዋንም የምታንቀሳቅሰው በመከራ ነው፡፡ በዚህ ላይ የሰመመን መድሀኒቱ ከሰውነቷ እስኪወጣና ተፈጥሮአዊ ሁኔታዋ በትክክል እስኪመለስ ድረስ ህጻኑ ወተት በጡጦ ወይንም በክዳን የሚሰጠው ሲሆን ከዚያ በሁዋላ ገና ያልለመደውን ጡት ይዞ ጫፍ አውጥቶ ወተት ለማግኘት ልጁም ትእግስት አይኖረውም፡፡ በህመም ላይ ያለች እናት ደግሞ የልጁዋን ጩኸት ለመስማት ስለማትፈልግ ወደ ጡጦዋ ትሄዳለች፡፡ ስለዚህ ይህ መስተካከል ያለበት ጉዳይ ነው ብለዋል ሁለቱም እናቶች፡፡ በእርግጥ የጡትን ጫፍ ማውጣት እና ልጅን እንዴት ማጥባት እንደሚቻል በእርግዝናው የመጨረሻ ወቅት እናቶች የሚለማመዱበት ሁኔታ ከወለዱ በሁዋላ ለነገሩ እንግዳ እንዳይሆኑ ስለሚያደርጋቸው ልጆቹንና ለችግር የእናት ጡት ወተት ለመመገብ ያስችላል፡፡ ስለዚህ ይህንን ሁሉም ልብ ሊለው ይገባል፡፡ ከዚህ በተረፈ ግን ማንኛዋም እናት ከማርገዝዋ በፊት እና በእርግዝናዋ ወቅት እንዲሁም ከወሊድ በሁዋላ ከሐኪም ክትትል መለየት እንደሌለባት ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡

Published in ላንተና ላንቺ
Page 7 of 16