ሌሊት አጎበር ስላለ ትንኟ የንክሻ ሰዓቷን ወደ ቀን አዘዋውራለች
(አቶ ገዛኢ አምባዬ፤ የባዝኦፍ አምራች ኩባንያ መስራችና ዳይሬክተር)
በሙያቸው አካውንታንት የሆኑት አቶ ገዛኢ አምባዬ፤ በ1964 ዓ.ም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውስጥ ተቀጥረው በሙያቸው መስራት እንደጀመሩ ይናገራሉ፡፡ በውሃና ፍሳሽ፣ በኢትዮጵያ ውሃ ስራዎች ድርጅትና በብረታ ብረት ኮርፖሬሽን በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ያገለገሉ ሲሆን በ1981 ዓ.ም ወደ ኬኒያ በማምራት የኢምፖርት ኤክስፖርት ስራ ላይ ከመሰማራታቸውም በተጨማሪ ባርና ሬስቶራንት በመክፈት ለረጅም አመታት መስራታቸውን ገልፀዋል፡፡ አንበሳ ባንክና ኢንሹራንስን ከመሰረቱት ሰዎች አንዱ የሆኑት አቶ ገዛኢ፤ ከ10 ዓመት በፊት ከውጭ ተመልሰው በአገራቸው መኖር ሲጀምሩ፣ ወባ በአገሪቱ ላይ እያደረሰ ያለውን ጥፋት መመልከታቸውን ያስታውሳሉ፡፡ ወባ በአፍሪካ እያደረሰ ያለውን ጥፋት በተመለከተ ጥናት ሰርተውም ለአሜሪካው ግዙፍ ኩባንያ IFF በመስጠት ተቀባይነት በማግኘታቸው፣ በለገጣፎ አካባቢ “ባዝኦፍ” የተሰኘ የወባ ትንኝ ማባረሪያ መድኀኒት በማምረት ላይ ይገኛሉ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ በመድኀኒቱና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከአቶ ገዛኢ አምባዬ ጋር ተከታዩን ቃለ-ምልልስ አድርጋለች፡፡


“ባዝኦፍ” የተባለውን የወባ ማባረሪያ ቅባት እንዴት ሊያመርቱ ተነሱ?
እኔ በ1981 ጀምሮ ወደ ጎረቤት አገር ኬኒያ ሄጄ ነበር፡፡ ከኢትዮጵያ ወይንና አምቦ ውሃ እየወሰድኩ ለኬኒያ፣ ለሩዋንዳ ለኡጋንዳና ብሩንዲ አከፋፍል ነበር። ኬኒያም ውስጥ “ግሪን” የተባለ ባርና ሬስቶራንት ነበረኝ፡፡ እዚያ እየሰራሁ እያለ IFF (International Flavors and Fragrance) የተባለ የአሜሪካኖች ትልቅ ኩባንያ ነበር፡፡ ይህ ኩባንያ ማጣፈጫዎችንና መዓዛማ ዘይቶችን ያመርታል፡፡ እነ ኮካ ኮላ፣ ለነ ፔፕሲና ሌሎችም ትልልቅ ኩባንዎች የሚያከፋፍል ነው፡፡ ከ10 ዓመት በፊት የዚህ ትልቅ ኩባንያ ወኪል ሆኜ ነው ወደ ኢትዮጵያ የመጣሁት። ሁኔታዎችን በማመቻቸት ስመላለስና እዚህ ቢሮ ስከፍት ግን 15 ዓመት ሆኖኛል፡፡ እናም እነሱ ጋር  በነበረኝ ግንኙነት ቸኮሌት፣ ከረሜላና መሰል ጣፋጮችን የሚያመርት ኩባንያ ለራሴ መክፈት አስቤ ስንቀሳቀስ፣ በወቅቱ ወባ በተለይ በአማራና በሌሎች ክልሎች የአገሪቱ ፈተና ሆኖ አየሁት፡፡ መነሻዬ ይሄ ነው፡፡
ከዚያ ምን አደረጉ?
በወቅቱ ወባ ህዝቡን እየፈጀች መሆኑን ከተለያዩ ሚዲያዎች አንብቤ ነው በጣም ያዘንኩት፡፡ ምን ይሻላል ምንስ ቢደረግ ህዝቡን መታደግ ይቻላል በሚል ራሴ በራሴ ትግል ውስጥ ገባሁ፡፡ አንድ ጥናት አጠናሁና “IFF” ላልኩሽ ኩባንያ አቀረብኩኝ፡፡ አፍሪካ የኮስሞቲክስም የሽቶም ችግር እንደሌለባት፣ በአሁኑ ጊዜ ሕዝቧ በወባ እያለቀ ስለመሆኑ፣ አምራች ኃይሉ በወባ ጥቃት እያለቀ እንደሆነ የሚያሳይ ነው ጥናቱ። ጥናቱን ተቀብለው ካዩት በኋላ “ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ፍሎሪዳ” አገሩም ወባማ ስለሆነ ቀድመው አጥንተው ነበር፡፡ ጥናቱን ያጠኑበትን ዋና መነሻ ሲነግሩኝም፤ “The Boston Tea Revolution” በነበረ ጊዜ የአሜሪካ ሰራዊት ያለቀው በወባ ነው፡፡ ያኔ ግን ወባ ነው ተብሎ በሽታው ተለይቶ አልታወቀም ነበር። የሆነ ሆኖ ጥናቱን ተቀበሉት፡፡ ከዚያ “ኢሴንሻል ኦይሉን” እንዲልኩልኝ አደረግሁኝ።
ኦይሉ ከተላከ በኋላ መጀመሪያ ጥናቱን የትኛው የአፍሪካ አገር አደረጉ?
መጀመሪያ ጥናቱ እንዲጠና የወሰንኩት ኬኒያ ነው፡፡ ምክንያቱም ኬኒያ ውስጥ “ኢሲፕ” የተባለ የዓለም ሳይንቲስቶች በሙሉ ስለ “ትሮፒካል ዲዚዝ” ጥናት የሚያደርጉበት ማዕከል ስላለ ነው። ከእነሱ ጋር ስምምነት በማድረግ፣ ከአሜሪካ የተላከው “ኢሴንሻል ኦይል” ከፔትሮሊየም ጄሊ (በተለምዶ ባዝሊን የምንለው) ጋር ተቀላቅሎ ቢሰራ በእርግጥ የወባ ትንኝን ያባርራል ወይ? የሚለውን እንዲያረጋግጡልኝ ነው ያደረግሁት። ብዙ ዶላር ካስከፈሉኝ በኋላ ጥናቱን ሰሩልኝ። ብዙ ዶላር የከፈልኩት ጥናቱ ሰፊ ስለሆነ ነው። አንደኛ የላብራቶሪ ሙከራ ያደርጋሉ፣ ሁለተኛ ወባ በተነሳ ጊዜ ገጠር ገብተው ካምፕ ሰርተው፣ ህዝብን አስተባብረው፣ ደም ምርመራ ያደርጋሉ። ምክንያቱም ጥናቱን የሚያካሂዱት በዓለም የጤና ድርጅት (WHO) መስፈርት መሰረት ስለሆነ ነው። ጥናቱ ወደ ሁለት ዓመት ገደማ ወስዶ፣ በመጨረሻ ምርምሩን አድርገን፣ሰ ቅባቱ “ባዝኦፍ” ከ 8 ሰዓት በላይ የወባ ትንኝ ያባርራል ሲሉ የምስክር ወረቀት ሰጥተውኛል፡፡ ይህ ከሆነ ወደ ስምንት ዓመት ገደማ ይሆነዋል፡፡
መድኀኒቱ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እውቅና አግኝቷል?
በሚገባ! እኔ ሰርተፍኬቱ ከተሰጠኝ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ሳመጣው፣ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ኃላፊዎች በጣም ተደስተው ነበር፡፡ እኔ ባዝኦፍን ወደ ኢትዮጵያ ባስገባሁበት ወቅት ሰዎች የሚጠቀሙት አጎበር በኬሚካል ያልተነከረ ስለነበር ብዙም ውጤታማ አልነበረም፡፡ ስለዚህ ጤና ጥበቃችሁ “ይህ መድኀኒት አማራጭ ስለሚሆነን አገር ውስጥ ያሉ የምርምር ተቋማት ለምን ጥናት አያደርጉበትም? ፓስተር ወይም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቢመራመሩበት ጥሩ ነው” አሉኝ፡፡
ምርምሩ ተካሄደ?
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲያጠኑት እንደገና ስምምነት አደረግን፡፡ “አክሊሉ ለማ የምርምር ማዕከል” የትሮፒካል ዲዚዝና የወባ ምርምር ማዕከል ነው፡፡ በዚህ መሰረት የላብራቶሪ ሙከራ ተደረገበት። ቆቃ አካባቢ ወባ ተነስቶ ስለነበር ዶክተሮቹ እዚያ ድረስ ሄደው ምርምርና ጥናት አድርገው፣ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ውጤቱ አመርቂ ነው በሚል ማረጋገጫ ሰጡኝ፡፡
ባዝ ኦፍ የሚመረትበት ፋብሪካ የት አካባቢ ይገኛል? በዓመት ምን ያህል ያመርታል?
ፋብሪካው ለገጣፎ ይገኛል፡፡ በጥሩ ሁኔታ እያመረትን ነው፡፡ አንደኛ ለፋርማሲዎች እናከፋፍላለን፤ ዋና የባዝኦፍ ተጠቃሚ ግን መከላከያ ሰራዊታችን ነው፡፡ ሰራዊቱ በፊት ከውጭ እያስመጣ ይጠቀም ነበር፡፡ እኛ ማምረት ከጀመርን በኋላ ከውጭ ማስገባታቸውን አቁመዋል፡፡ የተሻለ ጠቀሜታ አግኝተንበታል በማለት፣ በጀታቸው ውስጥ አስገብተው በየአመቱ ይወስዳሉ፡፡ ፌደራል ፖሊስም እንዲሁ እየወሰደ ነው፡፡ ሌሎች ተቋማትም መውሰድ ጀምረዋል፡፡ መንግስትም ይህንን በማየት ከወርልድ ባንክ ባገኘው ድጋፍ፣ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በኩል ወደ 103 ሺህ ዶላር ገደማ ድጋፍ አድርጎልናል፡፡ ይህ እርዳታ የተሻለ ምርምርና ጥናት ለማካሄድ እንዲሁም ኤክስፖርት ለማድረግ እንቅስቃሴ የሚውል ነው፡፡
እስካሁን ወደ ውጭ መላክ አልጀመራችሁም?
ጀምረናል፤ ወደ ናይጄሪያ፣ ኡጋንዳ፣ ሱዳን ሱማሌላንድና ሞቃድሾ ልከናል፡፡ሰ በአሁኑ ሰዓት ሌሎች የወባ ችግር ያለባቸው አገሮችም ምርቱን ለመውሰድ ጥያቄ እያቀረቡ ነው፡፡
“ኢሴንሻል ኦይሉ” ከአሜሪካ IFF እያስመጣችሁ ነው የምትጠቀሙት? ሌላስ ማቴሪያል ምንድን ነው የሚያስፈልጋችሁ?
ቤዙ እንዳልኩሽ ባዝሊን ነው፡፡ ባዝሊን ከውጭ ይመጣል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ከአንዳንድ ሳይንቲስቶች ጋር “ኢሴንሻል ኦይሉ”ን እዚሁ ለማምረት በምክክር ላይ ነን፡፡ አገራችን በርካታ ለመድኀኒትነት የሚያገለግሉ ሁሉም አይነት ዕፅዋት ስላላት ምቹ ናት፡፡ መድኀኒቱ ከእፅዋት ነው የሚሰራው፡፡ እነሱ የሰሩት ፎርሙላ ስላለን “ኢሴንሻል ኦይሉ”ን እዚሁ ለማምረት ዶክተሮቹን አጋር አድርገን ፋብሪካውን በማቋቋም ላይ ነን፡፡
ከረሜላና ቸኮሌት የሚያመርት ኩባንያም እንዳለዎት ሰምቻለሁ፡፡ ከባዝኦፍ ማምረቻው ጋር አንድ ላይ ነው ያሉት?
ቅርብ ለቅርብ ነበሩ፡፡ አሁን መለያየት ስላለባቸው እየለየናቸው ነው፡፡ በሁለቱም ኩባንያዎች ውስጥ አንድ የእንግሊዝ ኩባንያ በሽርክና ለመስራት መጥቷል፡፡ አሁን ከፍተኛ እንቅስቃሴ አለ፡፡ “ባዝኦፍን” ስናመርት በዚያውም ሽቶና መሰል መዓዛ ያላቸውን ምርቶችም እዚህ ለማምረት እያስመዘገብን ነው፡፡ አላማችን ከውጭ የሚመጡ የቼኮሌት፣ ከረሜላ፣ የወባ መድኅኒቶችና ሌሎችንም አስቀርተን አገር ውስጥ እንዲመረቱ ማድረግ ነው። እዚህ አምርተንና እሴት ጨምረን ኤክስፖርት ማድረግ ከኢኮኖሚም አኳያ አገሪቱን ይጠቅማታል፡፡
ባዝኦፍ ከስምንት ሰዓት በላይ የወባ ትንኝን እንደሚያባርር ተገልጿል፡፡ የመከላከል አቅሙ በመቶኛ ሲሰላ ምን ያህል ነው?
የዓለም የጤና ድርጅት አንድ መድኀኒት ከ60 እስከ 68 በመቶ መከላከል ከቻለ ውጤታማ ነው ይላል፡፡ ባዝኦፍ ግን 90 በመቶ አመርቂ ነው፡፡ ከስምንት ሰዓት በላይ እስከ 11 ሰዓት ድረስ ይሰራል። እየቆየ ኃይሉ እየደከመ እየደከመ ስለሚሄድ ግን በአማካኝ ከስምንት ሰዓት በላይ ይሰራል፤ በሚል እውቅና ተሰጥቶታል፡፡
አሁን አሁን በወባማ አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎች በኬሚካል የተነከረ አጎበር እየተጠቀሙ ነው፡፡ የባዝኦፍ ተጨማሪ ነው ወይስ እንዴት ነው?
አሁን ጥሩ ጥያቄ አመጣሽ፡፡ ሁሉም የተነከረ አጎበር ስለሚጠቀም፣ ሌሊት ትንኟ የሰዎችን ደም ማግኘት አልቻለችም፡፡ ስለዚህ የምትናከስበትን ሰዓት ቀይራለች፡፡ ለመኖርና እድሜዋን ለማራዘም ንክሻዋን ወደ ቀን አዘዋውራለች፡፡ የአሜሪካ ሳይንቲስቶችም ጥናት የሚያሳየው ይህንኑ ነው። ይህን በተመለከተ ሳይንቲስቶች በ6300 ሰዎች ላይ ጥናት ሲያደርጉ ለመጀመሪያው ቡድን አጎበር ብቻ ሰጡ፣ ለሁለተኛው ደግሞ መከላከያ ቅባቱንም አጎበሩንም ሰጡ፡፡ ውጤቱ ምን ሆነ መሰለሽ? አጎበሩንም መከላከያ ቅባቱንም የተጠቀሙ ሙሉ በሙሉ ከወባ በሽታ ነፃ ሲሆኑ አጎበሩን ብቻ ከተጠቀሙት መካከልብዙዎቹ በቀን እየተነከሱ የወባ ተጠቂ መሆናቸውን ያሳያል፡፡
አሁን ባዝኦፍን ተፈላጊ ያደረገው አንዱም ጉዳይ የወባ ትንኟ የንክሻ ሰዓቷን ወደ ቀን ማዛወሯ ነው፡፡ ቀን ቀን አጎበር ተሸክመሽ አትንቀሳቀሺም፤ ስለዚህ የግድ በወባማ አካባቢና በወባ ነሻ ወቅት ቀንም ባዝኦፍ መቀባት ግድ ነው፡፡
አሁን ክረምት እንደመሆኑ እስከ ህዳር ባለው ጊዜ ወባ በከፍተኛ ሁኔታ የሚቀሰቀስበት ወቅት ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት የምርታችሁ ተፈላጊነት ምን ይመስላል?
እንደነገርኩሽ በቋሚነት የሚወስዱ እንደ መከላከያ ሰራዊት ያሉ ተቋማት አሉ፡፡ ምርቱ በጣም ተፈላጊ ነው፡፡ አሁን ሁለቱም ፋብሪካዎች በ6500 ካ.ሜ ላይ ነው ያሉት፡፡ 15 ሺህ ካሬ ለባዝኦፍ ማስፋፊያ ጠይቀን እየጠበቅን ነው፡፡ ጉዳዩ አንገብጋቢና መንግስትን የሚያግዝ በመሆኑ ማስፋፊያው ሲፈቀድ፣ በስፋትና በጥራት ለማምረት ዝግጁ ሆነናል፡፡ አጋሮቻችን ብሩን ልከዋል፤ የገበያውን አዋጭነት፣ ላለፉት ዓመታት ሁለቱም ኩባንያዎቻችን የነበራቸውን ጉዳዮች መሰል ታሪኮች አስጠንተው ካመኑበት በኋላ ነው ገንዘቡን የላኩት፡፡
በመጨረሻ የሚሉኝ ካለ?
ያው ባዝኦፍ በዚህ መልኩ እየተመረተ ነው፡፡ ለወባ በሽታ በአማራጭነት በመቅረቡ መንግስትም ደስተኛ ነው፡፡ኤክስፖርት እየተደረገ የውጭ ምንዛሬም እያመጣ ነው፡፡ መከላከያው ትልቅ ፋይዳ ያለው ስለሆነ፣ ወደፊት የወባን በሽታ ሙሉ ለሙሉ ለመቅረፍ በምንችልበት አቅም ላይ እንድንደርስ በምርምሩም ሆነ በሁሉም ረገድ በርትተን እንሰራለን፡፡

Published in ዋናው ጤና

የማህበራዊ ሳይንስና የስነልቦና ባለሙያ
(ከአልታ ምርምር፣ሥልጠናና ካውንስሊንግ)

ሥነልቦናዊ ጤንነት ምንድነው?
ስነ ልቦናዊ ጤንነት  ስንል አንድ ሰው በስነልቦና አቋሙ ሊደርስበት የሚገባው የስሜት፣የአስተሳሰብና የባህሪ ደረጃ ነው፡፡ ይህም በአብዛኛው  ማህበረሰብ ሊከወንና ማህበረሰቡ ሊቀበለው የሚችለው ስነ ልቦናዊ አቋም ነው። ጤናማ ሲባል  በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ መካከለኛ የሆነው (average) ነገር ሲወሰድ ነው። ይህንን ትርጉም ለመረዳት ስነ ልቦናዊ ጤንነት ያላቸው ሰዎች ምን አይነት ስሜት፤አስተሳሰብና ባህሪ እንዳላቸው ለማየት እንሞክራለን፡፡
የስነ ልቦናዊ ጤንነት መለኪያዎች ምንድናቸው?
1. ራስን መውደድ(በመጠኑ ሲሆን)-Self-love (but not self-infatuation)
ራስን መቀበልንና ራስን መውደድን ወይም ለራስ ዋጋ መስጠትን ያመለክታል። ይህ ማለት ግን ከመጠን ያለፈ ራስን መውደድን ወይም ከመጠን ያለፈ ለራስ ዋጋ መስጠትን(self centeredness) አያካትትም። በመጠነኛ  ደረጃ ለራስ ዋጋ መስጠት(basic self esteem) አስፈላጊ ነው። ነገር ግን ከመጠን ያለፈ ለራስ ዋጋና ክብር መስጠት(unconditional self esteem) እንዲሁም ከመጠን ያለፈ ራስን መውደድ፣ በራስ ፍላጎት መያዝ (self infatuation) ለስነ ልቦናዊ ጤንነት አይመከርም። ስለዚህም ስነ ልቦናቸው ጤናማ የሆኑ ሰዎች ራሳቸውን  ይወዳሉ ወይም ማንነታቸውን ይቀበላሉ፤ ነገር ግን ራሳቸውን ከመጠን በላይ አይወዱም ወይም ከልክ ያለፈ ክብር ለራሳቸው አይሰጡም፡፡
2. ራስን ማወቅ-Self-knowledge
ስነልቦናዊ ጤንነት ያላቸው ሰዎች ራሳቸውን ያውቃሉ፡፡ እውነተኛ ስሜቶቻቸውንና የውስጥ ፍላጎቶቻቸውን ይረዳሉ። ሁልጊዜ ራሳቸውን የመፈተሻ ጊዜ አላቸው፡፡  ሶቅራጠስ የተባለው የግሪክ ፈላስፋ “ራስህን እወቅ” (know yourself) ከሚለው ሃሳቡ ጋር አብሮ ይሄዳል፡፡ አንዳንድ የስነ ልቦና ባለሙያዎች፤ ራስን መፈተሽንና ራስን ማወቅን ትኩረት ሰጥተው  እንዲመለከቱ “ደንበኞቻቸውን”  ያበረታታሉ።
ራስን ስለማወቅ ካነሳን የ ጆሃሪ ‘መስኮት’ን (Johari window) ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ ስብዕናችን አራት ክፍሎች እንዳሉት የሚጠቁም ሲሆን አንደኛው እኛ የምናውቀው ሰዎችም የሚያውቁት ማንነታችን ነው(open or free area)፡፡ ይሄ እንግዲህ የተገለጠ ማንነታችን ነው፡፡ ሁለተኛው እኛ የማናውቀው፣ ሌሎች ግን የሚያውቁት ማንነት ነው(blind area ይባላል)::  ሌላው እኛ ከሌሎች የደበቅነው ምስጢራችን ነው (hidden area) ይህም ማለት እኛ እናውቀዋለን፤ ሌሎች ግን አያውቁትም፡፡ የመጨረሻው እኛም ሌሎችም የማናውቀው ማንነታችን ነው (unknown area)፡፡ ይህ የመጨረሻው በተለይ በገጠመኞች ወይም በካውንስሊንግ ወይም በስልጠናዎች ብቅ የሚልና ለእኛና ለሌሎች የሚገለጥ ማንነት ነው። ያልተገለጠው አቅማችንም (potential) እዚህ አራተኛው የማንነታችን ክፍል ውስጥ ተደብቆ ነው የሚገኘው፡፡
 አንድ የስነልቦና ባለሙያ “ደንበኛው” ስለራሱ እንዲያውቅና አቅሙን እንዲያወጣ ይረዳዋል። ስነ ልቦናዊ ጤንነት ያላቸው ሰዎች ራሳቸውን ያውቃሉ፣ይረዳሉ፡፡
3. በራስ መተማመንና ራስን መግዛት-Self-confidence and self control
ስነልቦናዊ ጤንነት ያላቸው ሰዎች በራሳቸው መተማመን አላቸው። በግላቸው መስራት ያለባቸውን ማንንም ሳይፈልጉ ይሰራሉ፤ ከሌሎች ጋር ሆነው መስራት ያለባቸውንም ነገር ሃሳባቸውን በግልፅ በማቅረብ አብረው ይሰራሉ፡፡ ድርጊታቸውንና አካሄዳቸውን እንደሚቆጣጠሩት ያምናሉ፡፡ የብዙ ሰዎች ችግር የበታችኝነት ስሜት ነው፡፡ ሰዎች የበታችነት ስሜት እየተሰማቸው ከሄደ፣ ነገሮችን ሁሉ ከውጫዊ ምክኒያቶች ጋር የማያያዝ አባዜ ይጠናወታቸዋል፡፡ ይህም ማለት ገዢ ምልከታቸው (locus of control) ውጫዊ ይሆናል ማለት ነው፡፡
ሁለት አይነት ገዢ ምልከታዎች አሉ፡፡ እነዚህም የውስጥ (internal) እና የውጪ (External) ገዢ ምልከታዎች ይባላሉ:: የሰዎች ባህሪ በእነዚህ ሁለት ምልከታዎች ከፍተኛ ተፅእኖ ይደርስበታል፡፡ የእነዚህ ሁለት ገዢ ምልከታዎች ምንነትና በሰዎች አኗኗር ላይ የሚፈጥሩት ተፅእኖ ቀላል አይደለም፡፡
የውስጥ ገዢ ምልከታ(internal locus of control) ያላቸው ሰዎች በህይወታቸው ያሉ ስኬቶች የራሳቸው ጥረትና ውሳኔ ውጤቶች እንደሆኑ ያምናሉ፡፡ ባይሳካላቸው ደግሞ አስፈላጊውን ጥረት ባለማድረጋቸው እንደሆነ ያምናሉ፡፡ በዚህም ምክኒያት በህይወታቸው ለሚሆነው ነገር ሃላፊነትን ይወስዳሉ። እነዚህ ሰዎች የራሳቸው እሴትና እምነት ንግግራቸውንና ድርጊታቸውን ይወስናል። ለደረሱበትና ለሚገጥሟቸው ነገሮች  አግባብ የሆነ ሃላፊነትን ይወስዳሉ።
የውጪ ገዢ ምልከታ (external locus of control) ያላቸው ሰዎች በህይወት የሚገጥሟቸው ስኬቶች ወይም ውጤቶች የተገኙት በእድል ወይም ከነሱ በላይ በሆነና ከበረታ አካል እንደሆነ ያምናሉ(ለምሳሌ በማህበረሰቡ፣ በተቀጠሩበት ድርጅት፣ ወዘተ)፡፡ በዚህ ምክኒያት ለውድቀታቸውና ላልተሳካላቻው ነገር ሃላፊነትን አይወስዱም፡፡ ሃላፊነቱ የሌላው አካል ነው ብለው ያምናሉ። በዚህም ምክኒያት ለንግግራቸውና ለድርጊታቸው መሰረታዊ ምክኒያት የሌሎች ስሜት፣አመለካከትና እምነት ነው።  “ የእናቴ መቀነት አደናቅፎ ጣለኝ” እንደማለት ሰበበኛ ይሆናሉ፡፡ እኔ ግብ ስላላስቀመጥኩ፣ እኔ በትጋት ስላልሰራሁ፣ ላስቀመጥኩት ግብ እቅድ አውጥቼ ስላልተንቀሳቀስኩ፣ የሚፈለግብኝን ትኩረት ስላልሰጠሁ ወዘተ ይሄ ሆነብኝ አይሉም ማለት ነው፡፡ በተቃራኒውም ለድላቸው ወይም ለስኬታቸው የእነሱ ወሳኝ ሚና እንዳለ ስለማያምኑ፣ ራሳቸውን በመሸለም ደስታን አያጣጥሙም ማለት ነው፡፡
በሌላ በኩል ራሳቸውን የሚገዙ ሰዎች በተንኳሽና ምላሽ (stimulus-Response) አያያዛቸው ይታወቃሉ፡፡ተንኳሾች (Stimulus) በቃልና በድርጊት ወደ እኛ የሚመጡ ምላሽን (Response) የሚጎተጉቱ ወይም የሚፈልጉ ነገሮች ናቸው፡፡
ስቲቨን ኮቬይ የተባሉ ሰው ስለ ተንኳሽና ምላሽ ፅንሰ ሃሳብ በሰፊው ያብራራሉ፡፡ እኚህ ሰው እንደሚሉት፤ በተንኳሽና ምላሽ መካከል አንድ የማሰቢያ ነፃነት ስፍራ (space) አለ፡፡ ወደ ህይወታችን ተንኳሽ ሲመጣ ምላሹ ጥሩ ወይም መጥፎ እንዲሆን የምንወስነው በዚህ የማሰቢያ ነጻነት መጠቀም ስንችል ነው በማለት ያስረዳሉ።
አንድ  ተመሳሳይ ተንኳሽ  ወደ ሁለት ሰዎች በአንድ ጊዜ፣ በተመሳሳይ ቦታና ሁኔታ ቢመጣ የሁለቱ ሰዎች  በተንኳሹ መጎዳት ወይም መጠቀም የሚወሰነው  በአመዛኙ በተንኳሹ  ተፈጥሮ ሳይሆን ለተንኳሹ በሚሰጡት ምላሽ ነው፡፡  ለዚህም ነው በዚህ የተንኳሽና ምላሽ ፅንሰ ሃሳብ ትንታኔ፣ ሰው ተንኳሽ ሲገጥመው ለአፍታ “ቆም ብሎ” ምን ማድረግ እንዳለበት ማሰብ የሚገባው፡፡ እዚህ ላይ ልብ ማለት የሚያስፈልገው ተንኳሹን መቆጣጠር አለመቻላችንና መቆጣጠር የምንችለው ምላሻችንን መሆኑን ነው፡፡
በአመዛኙ ባህሪያችንን (የምንናገረውንና የምናደርገውን) የሚወስነው ወደ እኛ የሚመጣው ተንኳሽ  ሳይሆን ለተንኳሹ የምንሰጠው ምላሽ  መሆኑን ነው፡፡ እንግዲህ ተንኳሽ ሲመጣ ወይም ሊመጣ እንደሚችል ስንገምት የማሰቢያ ጊዜ ሊኖረን ያስፈልጋል፡፡ በዚህም ራስን የመግዛት አቅማችንን ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡ በመጽሃፍ ቅዱስም ላይ ከተማን ከሚገዛ ራሱን የሚገዛ እንደሚበልጥ ተፅፏል፡፡ ይህ እንግዲህ የሚያሳየው ከንቲባ ከመሆን ራስን መግዛት ምን አይነት ልዕልና እንደሆነ ነው፡፡
ስነ ልቦናዊ ጤንነት ያላቸው ሰዎች በራሳቸው ይተማመናሉ ራሳቸውንም ይገዛሉ።
4. ግልፅ የሆነና መጠነኛ ተስፋ ያለበት የተጨባጭነትን እይታ-A clear (though slightly optimistic) perception of reality
ስነ ልቦናዊ ጤንነት ያላቸው ሰዎች ገሃዱን ወይም ተጨባጩን ዓለም የሚያዩበት መንገድ ትንሽ ተስፋ ጠብ ያለበት ነው። በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ ተጨባጭነት (reality) ምንድነው? በሚለው ነገር ስምምነት አለ፡፡
ከዚህ ስምምነት በተለየ መልኩ ማፈንገጥ ስነ ልቦናዊ ችግር ነው ተብሎ ይታመናል። ሆኖም ስነ ልቦናዊ ጤንነት ያለው ሰው ስለ ራሱ አቅም(potenial) እና ስለ ወደፊት ህይወቱ መጠነኛ “አረንጓዴ መብራት” ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህም ተስፋ ማለት ነው-ከተጨባጩ ትንሽ አንድ እርምጃ መሄድ ያስፈልጋል፡፡ ተስፋ ባይኖር ህይወት ምን ትመስል ነበር? ለማሰብ ያስቸግራል፡፡
5. ድፍረትና ነገሮችን መቋቋም መቻል-Courage and resilience
ስነ ልቦናዊ ጤንነት ያለው ሰው የራሱን ፍርሃት የመቋቋምና ሃላፊነትን የመውሰድ ድፍረት አለው። አስፈላጊ ሲሆንም ምክኒያታዊነት ላይ የተመሰረተ ሪስክ ይወስዳል። አዲስን ሁኔታ መላመድ ይችላል፡፡ ከአስቸጋሪ ሁኔታዎችም (crises situations) ውስጥ ለመውጣት አቅም አለው። በተጨማሪም ጉድለቶችና ችግሮች በኑሮ ውስጥ ሊኖሩ እንደሚችሉ በማወቅ ድክመቶችንና ችግሮችን ተቀብሎ ለማሻሻል ወይም ለመፍታት ይጥራል እንጂ አንዳች ጉድ እንደመጣበት አያስብም፡፡ ከወደቁበት ተነስተው፣አቧራቸውን አራግፈው ሁሉን እንደ አዲስ እንደሚጀምሩ ሰዎች ነገሮችን የመቋቋም ችሎታ አለው፡፡
6. ሚዛናዊነት-Balance and Moderation
ሚዛናዊ ህይወት መኖር የስነ ልቦናዊ ጤንነት መኖር መገለጫ ነው፡፡ ስራና ጨዋታን፣ሳቅንና ለቅሶን፣ ስሜታዊነትንና ምክንያታዊነትን፣ ንፉግነትንና ለጋስነትን ወዘተ… ሚዛናዊ በማድረግ መኖር ጥበብም እንደሆነ ይነገራል፡፡ “ብልህ ሰው እንቁላሎቹን ሁሉ በአንድ ቅርጫት ውስጥ አያስቀምጥም” የሚለው አባባል ከሚዛናዊነት ጋር አብሮ ይሄዳል። አርስቶትል የተባለው የግሪክ ፈላስፋ፤ “ጥበብ ያለበት ምርጫ ሁለቱን ተቃራኒ ፅንፎች ትቶ መካከለኛውን መምረጥ ነው” ይላል። አብርሃም ማስሎውም(Abreham Maslow) ግለሰቦች ከተፃራሪ ፍላጎታቸው አንዱን ከመምረጥ ተቆጥበው ሁለቱን  ማስታረቅ ይጠበቅባቸዋል ይላል፡፡ ኪነር (Kinnier) በበኩሉ፤  መካከለኛን መንገድ በመምረጥ ግጭቶቻቸውን የሚፈቱ ሰዎች ፅንፍን ከሚይዙ ሰዎች ይልቅ ደስተኞች ናቸው ይላል፡፡ የሳይኮሎጂ አባት ተብሎ የሚጠቀሰውም ፍሮይድ(Freud) በግል ፍላጎትና በማህበረሰብ ፍላጎት መካከል ከፍተኛ ልዩነት በሚፈጠርበት ጊዜ ሚዛናዊነትን መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ገልጿል፡፡
በመሆኑም ስነ ልቦናዊ ጤንነት ያላቸው ሰዎች ሚዛናዊ ናቸው፡፡
7. ሌሎችን መውደድ-Love of others
ስነልቦናዊ ጤንነት ያላቸው ሰዎች ሌሎችን ይወዳሉ፡፡ በመፅሃፍ ቅዱስ ላይ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚለው ትዕዛዝ፣ ሁለት የስነ ልቦና ጤንነት አመልካቾችን በአንድ ላይ አጣምሮ የያዘ ነው፡፡ እነዚህም ከላይ በአንደኛ ደረጃ የጠቀስነውን ራስን መውደድና ይኸኛውን - ሌሎችን መውደድን። ሰው ራሱን ወድዶ ሌሎችን የማይወድ ከሆነ፣ የስነ ልቦና ጤንነቱ የተሟላ አይደለም፡፡
ስነልቦናዊ ጤንነት ያላቸው ሰዎች፤ ለሌሎች  ሰዎችና ለሰው ልጅ በአጠቃላይ ደህንነት(welfare) ለመጠንቀቅ አቅምና ፍላጎት አላቸው፡፡ ባርባራ ስትሪሳንድ  (Barbara Streisand) “ ሰዎችን የሚፈልጉ ሰዎች በዓለም ላይ በጣም ጤናማ ሰዎች  ናቸው” ይላሉ።
የዓዕምሮ ጤንነት ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎች፤ በቤተሰብና በማህበረሰብ መታቀፍና የመውደድ አቅም መኖር እንዲሁም ሌላውን ሰው መቅረብ፣ የስነ ልቦና ጤንነት ቅድመ ሁኔታ ነው ብለው ያምናሉ።
8. ህይወትን መውደድ-Love of Life
እርስዎ የተለያዩ የህይወት ገፅታዎችን ይወዳሉ? የስነ ልቦና ጤንነት ያላቸው ሰዎች ህይወት የያዘችውን የተለያዩ ገፅታዎች ያደንቃሉ፤ ደግሞም ይደሰቱበታል፡፡ እነዚህ ሰዎች ንቁ፣ጉጉና በተለያዩ የህይወት ገፅታዎች የሚደነቁ ናቸው፡፡ ህይወትንም ለመማር፣ ለማደግና ከሌሎች ጋር የተለያዩ ነገሮችን አብሮ ለመካፈል እድል የምትሰጥ ናት ብለው ይደሰቱባታል፡፡ እነዚህ ሰዎች “ እግዚአብሄር የሰራት ቀን ይህቺ ናት፤ ሃሴትን እናድርግ፤ በእርሷም ደስ ይበለን” እያሉ በማለዳ ተነስተው ወደ ተሰጣቸው ቀን የሚገቡ ይመስላሉ።
9. በዓላማ መኖር-Purpose of life
ስነ ልቦናዊ ጤንነት ያላቸው ሰዎች በዓላማ የሚኖሩ ናቸው፡፡ ትርጉም ያለውና ግብ ያለው ኑሮ የሚኖሩ ናቸው፡፡ በኑሮ ውስጥ ትርጉም አጥቶ መኖር ደስታን ያሳጣል፣ተስፋንም ያጨልማል፡፡
“ማሞ ቂሎ”  መንገድ ጀምሮ ሲሄድ ሲሄድ፣ አንድ መንታ መንገድ ላይ ደረሰና ቆመ፡፡ በአጋጣሚ “ስንዝሮን” አገኘውና “ የትኛውን መንገድ ልከተል?” አለው  ስንዝሮም “ የት ለመሄድ ፈልገህ ነው?”
ማሞ ቂሎም “ አይ አላውቀውም” ብሎ መለሰለት፡፡ስንዝሮም ቀበል አደረገና “ የትኛውንም መንገድ ብትከተል ያደርስሃል፡፡” አለውና ጥሎት ሄደ ይባላል፡፡ ዓላማ ይዞ የማይኖር ሰው፣ ልክ እንደ ማሞ ቂሎ መሄዱን እንጂ የት መድረስ እንደሚፈልግ አያውቀውም፡፡ አንዳንድ ሰው የት እንደሚሄድ ሳያውቅ፣በቀን ውስጥ ማንን እንደሚያገኝ ሳይወስን ከቤት የሚወጣበት ሁኔታ አለ፡፡ ወደ ሳሪስ መንገድ ጀምሮ ድንገት መኪና ሲያገኝ መዳረሻው ፒያሳ ሊሆን ይችላል፡፡ “ ራዕይ የሌለው ህዝብ መረን ይወጣል” ተብሎ ተፅፎ የለ!
የተከበራችሁ አንባቢያን፡- በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በዓለም ላይ የስነልቦና ችግር እንዳላቸውና በየዓመቱ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ራሳቸውን እንደሚያጠፉ የዓለም ጤና ድርጅት ገልጿል፡፡ ከላይ የተጠቀሱትን የስነ ልቦና ጤንነት መገለጫዎች በመገንዘብና የአዕምሮ ደህንነታችንን በመጠበቅ የተሻለ ስብዕና ባለቤት እንሁን፡፡
ቸር እንሰንብት!
ፀሐፊውን ኢ-ሜይል አድራሻው፡ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል

Published in ዋናው ጤና

የ95 ዓመት አባት አርበኛ ናቸው፡፡ ያልዘመቱበት የጦር አውድማ የለም። በዚህ ዕድሜያቸው ከ70 ዓመት በፊት የተደረጉ ጦርነቶችን ከእነ ዓመተምህረታቸው ያስታውሳሉ፡፡
ባለፈው ሳምንት በኢኮኖሚና ንግድ አምድ ላይ ቃለምልልስ የተደረገላቸው “የባላገሩ አስጐብኚ ድርጅት” ባለቤት፣ አባት አርበኞችን ወደ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ወስዶ የማስጐብኘት ሃሳብ የመጣላቸው በእኚህ አዛውንት ጥያቄ መሆኑን ገልፀውልናል፡፡
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛዋ ናፍቆት ዮሴፍ ከእኚህ የዕድሜ ባለፀጋ አባት ጋር ማራኪና አዝናኝ ቃለምልልስ አድርጋለች። እነሆ:-



ስምዎትን ያስተዋውቁኝ አባት…
ሃምሳ አለቃ ደምሴ ፀጋዬ እባላለሁ፡፡ ትውልድና እድገቴ ወሎና ጎንደር ነው፡፡ በአንድ ጎን ደባት ገብርኤል ነኝ፡፡ በሌላ ጎኔ ደግሞ ወሎ ውስጥ የጁ እና ላስታ ነው እድገቴ፡፡ ጠቅለል ስታደርጊው ዘር ሃረጌ ከወሎ እና ከጎንደር ይመዘዛል ማለት ነው፡፡
እስቲ ስለልጅነት ያጫውቱኝ?
እንዴ! የአስተዳደጌ ሁኔታማ ምን ይወራል። የተወለድኩት በ1911 ዓ.ም ታህሳስ 3 ቀን ነው፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምረሽ እድሜዬን ማስላት ትችያለሽ፡፡ ጠላታችን ጣሊያን መጥቶ አባቶቻችን ሲዘምቱ የ18 ዓመት አፍላ ጎረምሳ ነበርኩኝ፤ በ1928 ዓ.ም ማለት ነው፡፡ አባቴ በውጊያው ቆስሎ ነበር ከዘመቻው የተመለሰው፡፡
የት ቦታ አባትዎ እንደቆሰሉ አልነገሩዎትም?
ነግሮኛል! ማይጨው ላይ ነው የተመታው፡፡ የዘመተው ከደጃዝማች አድማሱ ብሩ ጋር መሆኑንም አጫውቶኛል፡፡ ደጃዝማቹ እዚያው በውጊያው ሲሞቱ፣ አባቴ ግን ቆስሎ መጣ፡፡ የማስታውሰው እኔ የ19 ዓመት ወጣት ስለነበርኩ፣ አባቴ ውጊያ ሲሄድ የእርሻውን ስራ እኔ እሸፍን ነበር፡፡ አባቴ ከውጊያ የመጣ ቀንም ሞፈርና ቀንበሬን አነባብሬ እርሻ ወርጄ ማሽላ ስዘራ ነበር የዋልኩት፡፡ እነሱ ሲመጡ ጥይቱ እንደ ማሽላ ቆሎ… ጣ  ጣ   ጣ  ጣ ይላል፡፡ ምንድን ነው ነገሩ ብዬ ስጠይቅ፤ “አባትሽ መጣ” አሉኝ፤ አንቺ ነበር የሚሉኝ፡፡
ለምንድነው አንቺ የሚልዎት?
ምክንያቱ በግልፅ አይገባኝም፡፡ ስገምት ግን ስራመድ ከእግሬ እንደ ሴት ፈጠን እላለሁ፡፡ ለዚያ ይመስለኛል፡፡
ከዚያስ?
ከዚያማ ማሽላውን ዘርቼ ጨርሼ፣ ሞፈርና ቀንበሩን እዚያው ትቼ፣ መዋጆውን ይዤ በሬዎቼን እየነዳሁ ነበር፤ ወደ ቤት ለመግባት፡፡ በኋላ አባትሽ መጣ ሲሉኝ፣ መዋጆውንም በሬውንም ትቼ በሩጫ ወደ ቤት መጣሁ፤ ስደርስ አባቴን አገኘሁት፡፡
በጣም ተጎድተው ነበር?
በጣም እንጂ! ሚያዚያ ወር ላይ ነበር የመጣው፡፡ ከዚያ ግንቦት፣ ሰኔ፣ ሐምሌ እና ነሐሴን አስታመምነው፡፡ ከተሻለው በኋላ አሁንም የጠላት ጦር እያየለ ሲመጣ፣ “አገሬ ተወርራ አልቀመጥም” ብሎ ታላቅ ወንድሙን፣ የመጀመሪያ ልጁን (ታላቄን)፣ እኔን አስከትሎ ከአንድ ቤት አራት ሆነን ዘመትን!! ታች ጋይንት አርብ ገበያ ላይ በተደረገው ጦርነት ህዝብ አለቀ፡፡ ከላይ በአውሮፕላን እንደበደባለን፣ በመሬት ይህ ነው ብዬ በቁጥር የማልጠቅሰው እስከ አፍንጫው የታጠቀ የጣሊያን ወታደር አለ፡፡ ምን አለፋሽ… ምድር ቃጤ ሆነች፡፡ እኔ ነጭ ቃታ ቤልጂግ ይዣለሁ፣ አባቴ ረጅም ለበን የሚባል መሳሪያ ይዟል። አባቴ ጥይት ሲያልቅበት አፈሙዙን ድንጋጥ ሰብሮ መሃል ገባ፡፡ ይህን ነጫጭባ ሁላ አንጀት አንጀቱን ዘክዝኮ ዘክዝኮ ከጣለ በኋላ፣ እሱም ወንድሙም፣ የመጀመሪያ ልጁም እዚያው አለቁ (ሲያወሩኝ ስሜታቸው እየጋለ ነው)
እርስዎም በምን ተዓምር ተረፉ ታዲያ?
እኔ አብሬ መሞት ፈልጌ ነበር፡፡ ሰዎች “አንተ እንኳን ትረፍ” በሚል ወደ ኋላ ጎተቱኝና ከእነሱ ጋር አፈገፈግን፡፡ ከዚያ ተርፌ አምስቱን አመት ጣሊያን ከአገራችን እስኪወጣ ተዋግቼ ይኸው እዚህ ደረስኩኝ፡፡
ኮሪያ ዘምተዋል እንዴ?
እንዴታ! ኮሪያና የኤርትራ ዘመቻ አንድ ቀን ነው የዘመትነው፡፡ በወቅቱ ኤርትራ በፌዴሬሽን ነበር የምትተዳደረው፡፡
ራስ ገዝ ነበረች አይደል?
አዎ! ከዚያ በኋላ ከእኛ ጋር ተቀላቀለች፡፡ ይህ እንግዲህ በ1973 ነው፡፡ ከዚያ በኋላ “ወርቋ ኤርትራ ከእናቷ ኢትዮጵያ ጋር በሰላም ተቀላቀለች” ተባለ። ወታደሮቹና ኤርትራዊያኑ አምስት ቀን ሙሉ አብረውን ሲበሉና ሲጠጡ ቆይተው ጃንሆይ ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ፣ እኛ ወደ ምፅዋ ልንወርድ ስንል መንገድ ላይ ጠብቀው አይጠምዱንም መሰለሽ! አስቢው… ሁለት ሻምበል ጦር ወደፊት ሄዷል፡፡ የመሳሪያ ግምጃ ቤቱንና ጠቅላይ ሰፈሩን ሰዎች ከሁለት ቆርጠው ተኩስ ከፈቱብን፡፡
ከኢትዮጵያ ጋር ተቀላቀለች ከተባለ በኋላ ነው?
ታዲያስ! አብረውን በልተው ጠጥተው… የሻዕቢያ ነገር ተመልከቺ! ከዚያ እኔም በሁለት ጥይት ተመትቼ ወደቅኩኝ፡፡
ተጐድተው ነበር?
ታፋዬን ነው የተመታሁት፡፡ ከዚያ በኋላ የሆነውን የተደረገውን አላውቅም፤ ራሴን ስቼ ነበር፡፡ በኋላ ስነቃ አብረውኝ የነበሩት በመትረየስ ጭንቅላታቸውን ተመትተው እኔ ላይ ወድቀዋል። ሬሳ ሲነሳ እኔ ከእነ ነፍሴ ተገኘሁ፡፡ የሚያውቁኝ ሰዎች “አሞራዋ በነፍስ አለች” ብለው እኔን ጨምሮ ሰባት ቁስለኛ በሄሊኮፕተር ተጭነን፣ አዲስ አበባ ምኒልክ ሆስፒታል ገባን፡፡ ሁለቱ ጓዶቻችን ሆስፒታል እንደደረሱ ሞቱ፡፡ አምስታችን ተረፍን፡፡
ሆስፒታል ምን ያህል ጊዜ ለህክምና ቆያችሁ?
አንድ አመት ከዘጠኝ ወር ያህል ሆስፒታል ቆይተናል፡፡ ከዚያ በየቦታው አንድ አንድ ጋሻ መሬት ተሰጠን፡፡ ለእኔ ጉራጌ ዞን ጨወና ወረዳ፣ አመያ የተባለ ቦታ ደረሰኝ፡፡ ያንን መሬት ስቃበጥበት ኖርኩኝ፡፡
የትዳር ህይወትዎ ምን ይመስላል? ልጆችስ ወልደዋል?
ልጆች ወልደዋል ወይ ነው ያልሽው? ያውም በቁና ሙሉ ነዋ! ትዳር ይዤ መውለድ የጀመርኩት በ1937 ዓ.ም ነው፡፡ 19 ልጆች ወልጃለሁ፡፡
ሁሉም በህይወት አሉ?
19 ልጆች ወልጄ አሳድጌ ነበር፡፡ አምስቱ ሞቱብኝ፡፡ አሁን 14 ልጆች፣ 18 የልጅ ልጆች፣ ብዙ የልጅ ልጅ ልጆች አሉኝ፡፡ ከቅድመ አያትም እስከ ምንጅላትነት ደርሻለሁ፡፡
እንደ እርስዎ አርበኛ የሆነ የሆነ ልጅ አለዎት?
አይይይ…….የለኝም፡፡ ወደፊት አርበኛ ይሆኑ እንደሆነ እንጂ እስካሁን የለኝም፡፡
ሶማሊያ ኢትዮጵያን ስትወርር ዘምተዋል?
እንዴ ምን ነካሽ… በደንብ እንጂ! በኦጋዴን ዘጠነኛ ማካናይዝድ ጦር ውስጥ ነበርኩኝ፡፡ ይህ ሁሉ አልፎ መጨረሻ አካባቢ ጡረታ ልወጣ ስል አዲስ አበባ መጣሁ፡፡ በመከላከያ ሚኒስቴር በደሞዝና መዝገብ ቤት ተቀጥሬ ስሰራ ቆይቻለሁ፡፡ በሂሳብ አስተዳደርና በመዝገብ አያያዝ ባለሙያ ሆኜ ነው የሰራሁት፡፡
ተምረዋል ማለት ነው?
እስከ ስድስተኛ ክፍል ተምሬ ሚኒስትሪ ወስጃለሁ፡፡ በየነ መርዕድ ት/ቤት ነው የተማርኩት። እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ ከዚያ በኋላ በርካታ መስሪያ ቤቶች ሰርቻለሁ… ይገርምሻል!
አሁን በጥንታዊት ኢትዮጵያ አርበኞች ማህበር ውስጥ ተሳትፎም ምንድነው?
በፊት በሌላ ኮሚቴ ውስጥ እሰራ ነበር፡፡ አሁን የመቃብር ኮሚቴ ነኝ፡፡
በጡረታ ደሞዝ ነው የሚተዳደሩት?
ጡረታም አለኝ ግን ብዙ ልጆቼ ከውጭ በየአቅጣጫው ብር ይልካሉ፤ የብር ችግር የለብኝም። ከባለቤቴ ጋር ዘና ብዬ ተደስቼ ነው የምኖረው፡፡
እድሜዎ 95 ዓመት እንደሆነ ነግረውኛል፡፡ ግን ሙሉ ጥርስ፣ ሙሉ ጤና አለዎት፡፡ አመጋገብዎ እንዴት ነው?
የተገኘውን እበላለሁ፤ መጠጥ ድሮም አሁንም በአፌ አይዞርም፤ ውሃ ብቻ ነው የምጠጣው፡፡ ጥሬ ስጋ ድሮ እበላ ነበር፤ አሁን ለጤና ጥሩ አይደለም ስለሚባል ትቻለሁ፡፡
የታላቁን የህዳሴ ግድብ ለመጎብኘት ከፍተኛ ጉጉት እንዳለዎት ሰምቻለሁ…?
ወይ ልጄ ሁሉም በየጊዜው በየትውልዱ ታሪክ ይሰራል፡፡ በእኛ ትውልድ ያለ በቂ መሳሪያ በጦርና በጎራዴ ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀውን ጣሊያንን አሳፍረናል፡፡ አክሱምን፣ ላሊበላን፣ ጎንደርን ገንብተው ያለፉ ትውልዶች አሉ፡፡ ይሄ ትውልድ ደግሞ ለም አፈር አዝሎ ሲጓዝ፣ ሌላ አገር ሲያለማ የነበረውን አባይን ሲገድብ እድሜ ሰጥቶኝ ከደረስኩ እንዴት አልጓጓ? ግድቡን ጠዋት ጎብኝቼ ማታ ብሞት ደስታውን አልችለውም፡፡
ከዚህ በኋላ ስንት ዓመት መኖር ይፈልጋሉ?
እየውልሽማ… እግዚያብሔር ለአብርሃም 500 ዓመት ሲሰጠው፣ ለዚህች አጭር እድሜ ብዬ ቤት አልሰራም ብሎ በድንኳን ኖረ፡፡ እኔ አሁን ወደ 95 ዓመት እየሄድኩ ነው፡፡ ለእኔስ 150 ዓመት ቢሰጠኝ ምን ይለዋል? (ረጅም …..ሳቅ)

Published in ህብረተሰብ

ፓርቲዎች የየራሳቸውን የቢሮ  ህንፃ እንዲገነቡ የባንክ ብድር ተፈቀደላቸው
ተቃዋሚዎች በየሳምንቱ የ60 ደቂቃ የቴሌቪዥን አየር ሰዓት ተመደበላቸው
በ“ሽብር” የታሰሩ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች በምህረት ተለቀቁ  

ቀኑንና ዓመተ ምህረቱን አላስታውሰውም፡፡ እለቱ ግን አርብ ነው፡፡ እኔ ቢሮዬ ውስጥ ነው ያለሁት፡፡ “ፖለቲካ በፈገግታ”ን እየፃፍኩ፡፡ አልፎ አልፎ በመስኮት በኩል የማየው ሰማይ ሰፊ ባህር ይመስላል፡፡ በጋዜጣው ዝግጅት ክፍል እንደወትሮው ወከባ አይታይም፡፡ ጋዜጣው የሚወጣበት ቀን ግን አልተለወጠም - ያው ቅዳሜ ነው፡፡
አንጋፋው የግል ጋዜጣ፣ከአንጋፋው ማተሚያ ቤት ከብርሃንና ሰላም ጋር ከተለያየ ጥቂት ወራት  ተቆጥረዋል፡፡ አሁን ጋዜጣው የሚታተመው በራሱ ማተሚያ ቤት ነው፡፡ እጅግ ዘመናዊና ደረጃውን የጠበቀ የህትመት ማሽን አስመጥቷል - 100 ሺ ኮፒ በ30 ደቂቃ ውስጥ አትሞ የሚገላግል፡፡ ለዚህ ነው አርብ አርብ ወከባ የቀረው፡፡
አዲስ አድማስ ብቻ ሳይሆን አብዛኞቹ የግል ጋዜጦች የራሳቸው ማተሚያ ማሽን አስገብተዋል (እንደነ “ዋሽንግተን ፖስት” ወግ ደረሰን!) ጋዜጦች የሚሸጡት እንደ ድሮው ጎዳና ላይ አይደለም፡፡ ራሳቸው ባዘጋጁት ቄንጠኛ ኪዮስኮች ውስጥ ሆኗል፡፡ ከሁሉም የሚገርመው ግን በጋዜጦች የስርጭት መጠን (ኮፒ) ላይ የታየው ለውጥ ነው፡፡ በሳምንት ከ100 ሺ በታች ቅጂዎች የሚያሳትም ጋዜጣ ፈልጎ ማግኘት አይቻልም፡፡ (አትጠራጠሩ! የማወራው ስለ ኢትዮጵያ ነው!)  አብዛኞቹ ጋዜጦችም ከኪራይ ቢሮ ወጥተው ራሳቸው ባስገነቡት ባለአምስትና ስድስት ፎቅ ህንፃ ውስጥ ገብተዋል፡፡ ኢህአዴግ ቁጥር 1 የግል ፕሬሱ አጋር ከሆነ ከራርሟል፡፡ የማተሚያ ማሽን ከቀረጥ ነፃ እንዲገባ ከመፍቀዱም ባሻገር ለሁሉም የግል ጋዜጦች የህንፃ መስሪያ ቦታ በነፃ አከፋፍሏል፡፡ ባይገርማችሁ ለማመን እሚያዳግቱና ትንግርት የሚመስሉ ለውጦች እየታዩ ነው፡፡
ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለምርጫ ሰሞን በስንት ውዝግብ ያገኙት የነበረው የቴሌቪዥንና ሬዲዮ የአየር ሰዓት አሁን በሽበሽ ሆኗል፡፡ (“ኢህአዴግ ለብቻው ሲጠቀምበት የኖረውን ሚዲያ ለህዝብ ጥቅም ሲባል  ተቆጣጥረነዋል” አልተባለም እንጂ!) የምርጫ ሰሞን ብቻ ሳይሆን በአዘቦት ቀንም እያንዳንዱ ተቃዋሚ ፓርቲ በሳምንት አንድ ቀን የ60 ደቂቃ የአየር ሰዓት ተመድቦለታል፡፡ በኢህአዴግ ችሮታ አሊያም  በተቃዋሚዎች ትግል የተገኘ አይደለም፡፡ ሁለቱም ተስማምተው ባፀደቁት አዲስ የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ ላይ ተደንግጓል፡፡ ይሄ ለማመን እንደሚቸግር ይገባኛል - ግን ግዴለም እመኑት፡፡ (“እቺ ናት አገርህ” አለ ገጣሚው!) ይሄ ብቻ ግን አይደለም፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ እላይና እታች ማለት  ቀርቶላቸዋል፡፡ ከእነሱ የሚጠበቀው ከ24 ሰዓት በፊት ለሚመለከተው ወገን በኢ-ሜይል ማሳወቅ ብቻ ነው፡፡ “የስብሰባ እንጂ የቅስቀሳ ፈቃድ የላችሁም” በሚል ከየመንገዱ ሰብስቦ ማሰር መልሶ ያሳስራል፡፡  
እንዲያም ሆኖ ግን ሰላማዊ ሰልፍ በሽበሽ አይደለም፡፡ ከስንት አንዴ በናፍቆት የሚታይ “ብርቅዬ ነገር” ሆኗል፡፡ ተቃዋሚዎች ችግራቸውን ከኢህአዴግ ጋር በመወያየት መፍታት ስለጀመሩ ህዝቡን ለሰላማዊ ሰልፍ መጥራት እርግፍ አድርገው ትተዋል፡፡ ብቻ ምን ልበላችሁ? ኢትዮጵያ የምታስቀና አገር ሆናለች፡፡ በርካታ የአፍሪካ አገራት ፖለቲከኞች እንደ ውሃ ቀጂ  ይመላለሱባታል - የፖለቲካ ልምድ ለመቅሰም፡፡  
የስብሰባ አዳራሽ ፍለጋ ከአንዱ ሆቴል ሌላው ሆቴል መኳተንም ተረት ሆኗል፡፡ “ስብሰባችንን ባለ 5 ኮከብ ሆቴል ውስጥ ነው የምናካሂደው” ካላሉ በቀር የህዝብ አዳራሾች ለእነሱም ለኢህአዴግም እኩል አገልግሎት እንዲሰጡ በአዋጅ ተደንግጓል፡፡
 የጋዜጣችን ሪፖርተር፤ በኢህአዴግ ጉባኤ ላይ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ በክብር እንግድነት መጋበዛቸውን ሰምታ መገረሟን ነገረችኝ (እሷ የምታውቀው የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ አባላት ሲጋበዙ ነዋ!) ለነገሩ እኔም የአገሪቱ ጠ/ሚኒስትር በተቃዋሚ ፓርቲ የምስረታ በዓል ላይ ተገኝተው ንግግር ማድረጋቸውን በኢቴቪ አይቻለሁ፡፡ ያኔ ነው ተቃዋሚዎች ለቢሮ የሚያገለግላቸው ህንፃ እንዲገነቡ ከባንክ ብድር የተፈቀደላቸው፡፡  
ምርጫ በመጣ ቁጥር ለፓርቲዎች ውዝግብ መነሻ የሚሆነው “የምርጫ ቦርድ” መፍትሄ እንደተገኘለት ኢህአዴግና ተቃዋሚዎች በጋራ ባወጡት መግለጫ ማስታወቃቸውም የ“ህዳሴው አብዮት” አካል ነው ተብሏል፡፡ መግለጫው እንደሚለው፤ቦርዱን ከገዢው ፓርቲና ከተቃዋሚ ፓርቲዎች የተውጣጡ አባላት እንዲመሩት ተደርጓል (“አሹ” አላላችሁም!) የህዳሴው ፍሬ ገና አላለቀም፡፡ እንደውም የበለጠ የሚያስገርሙና አፍ የሚያሲዙ ጉዳዮች  ይቀራሉ (የልብ ችግር ያለባችሁ ጠንቀቅ በሉ!)   
በቅርቡ… ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከመንግስት ጋር ተደራድረው “በሽብርተኝነት” ተከሰው የተፈረደባቸው ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞችን ጨምሮ በርካታ እስረኞች በምህረት ተለቀዋል፡፡ (የሰለጠነ ዘመን ይሏል ይሄ ነው!) እዚያው ቢሮዬ ውስጥ እንደተቀመጥኩ ኢቴቪ ሰበር ዜና (breaking news) ሲል ሰማሁና ቀና ብዬ መመልከት ጀመርኩ፡፡ ኢህአዴግ መራሹ መንግስት፤ በፓርላማ “ሽብርተኛ” ተብለው ከተፈረጁ የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል አልቃይዳና አልሸባብ ሲቀሩ ለሌሎቹ ምህረት ማድረጉን አስታወቀ፡፡ ለተለያዩ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት ጠ/ሚኒስትሩ፤ “በሽብርተኝነት ለተፈረጁት የፖለቲካ ድርጅቶች ምህረት የተሰጠው ከትጥቅ ትግል ወጥተው ወደ ሰላማዊ ትግል በመግባት ለእናት አገራቸው በጎ አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ ይችላሉ በሚል እምነት ነው” ብለዋል (“ለሁሉም ጊዜ አለው” አለ ጠቢቡ ሰለሞን!)
ኢህአዴግ ለበርካታ ዓመታት “ዓይንህ ለአፈር” ሲለው የነበረው (በአሮጌው ዘመን ማለቴ ነው!) ሂዩማን ራይትስ ዎች የተባለ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድን፤ የኢትዮጵያ መንግስትን የሰብዓዊ መብት አያያዝ የሚያደንቅ ጉደኛ ሪፖርት አወጣ፡፡(“ዘይገርም” እኮ ነው!) የመንግስት ኮሙኒኬሽን ፅ/ቤት ሚኒስትሩ በበኩላቸው “በእውነተኛ የህዳሴ አብዮት የተፈጠረችው ኢትዮጵያ ብዙዎችን እያስደመመች ነው” ሲሉ በፌስ ቡካቸው ላይ ፅፈው አነበብኩ፡፡ (እንኳን የአዳም ዘር ፈጣሪም ተደምሞባታል!) እስካሁን የተረኳት ዓይነት ኢትዮጵያ ገና አልተፈጠረችም፡፡ ሌላው ቀርቶ ኢቴቪም እንኳ አያውቃትም፡፡  ሰሞኑን እቺን ህልም የምትመስልና የምታስቀና ኢትዮጵያ ለመፍጠር የሚያስችል አዲስ ፕሮፖዛል ስቀርፅ ነው የሰነበትኩት። የፕሮፖዛሌን ዝርዝር በጥሞና ተከታተሉኝ፡፡ የዚህን ፕሮፖዛል መነሻ ሃሳብ ያገኘሁት “Trance” ከተሰኘው ፊልም ላይ እንደሆነ ለመግለፅ እፈልጋለሁ (የኮፒራይት መብት ለማክበር ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል እስክትሆን መጠበቅ የለብንም!) እናላችሁ… በአዲሱ ፕሮፖዛሌ መሰረት ከላይ የተገለፀችውን የህልም ዓለም የምትመስል ኢትዮጵያ ለመፍጠር እያንዳንዱ ፖለቲከኛ (ገዢውንም ተቃዋሚዎችንም ይመለከታል!) ከስልጣን ሱስ ሙሉ በሙሉ መላቀቅ ይኖርበታል፡፡ ለእስከዛሬው የአገራችን የፖለቲካ ቀውስ ሰበቡ ሌላ ሳይሆን ሥልጣንና ሥልጣን ብቻ እንደሆነ ፕሮፖዛሌ ይጠቁማል፡፡ ስለዚህ የአገሬ ፖለቲከኞች ሃሳባቸውንም ሆነ ስሜታቸውን ከስልጣን ማላቀቅ አለባቸው፡፡ በቃ ሥልጣንን እርስት ያደርጉታል፡፡ ይሄ ግን በራስ ጥረት ብቻ የሚሳካ አይደለም፡፡ በ “Trance” ፊልም ላይ ሳይመን ከቁማር ሱስ (gambling addiction) ለመገላገል  ወደ ቴራፒስት ዘንድ እንዳመራው ሁሉ፣ ፖለቲከኞቻችንም ተመሳሳይ ህክምና (ቴራፒ) ማግኘት እንዳለባቸው በአፅንኦት ይገልፃል - ፕሮፖዛሌ፡፡ (ሥልጣን ከቁማር የባሰ ሱስ ነው!)እናም ፖለቲከኞች በሂፕኖቴራፒ---- የሰመመን ዓለም ውስጥ እንዲገቡ ተደርገው ሥልጣን የሚለው ፅንሰ ሃሳብ ከአዕምሮአቸው ውስጥ ይወጣል፡፡ ስልጣን ላይ ያሰፈሰፈ አዕምሮአቸው በምትኩ በአገር ፍቅር… በሰብዓዊ መብት አከባበር… በልማትና ብልፅግና ላይ ብቻ እንዲያተኩር ይደረጋል። በሌላ አነጋገር “ሂፕኖታይዝድ” ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ ቴራፒውን በተከታታይ ወስደው በስኬት ሲያጠናቅቁም  ከስልጣን ጋር የማይተዋወቁ ፖለቲከኞች ሆነው ቁጭ ይላሉ፡፡ ቴራፒው ሥልጣንን ያብሰለስል የነበረውን የአዕምሮአቸውን ክፍል በሰረገላ ቁልፍ ይከረችመዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ሥልጣን ለእነሱ የማያውቁት አገር ሆነ ማለት ነው፡፡ (“ጅብ የማያውቁት አገር ሄዶ ቁርበት አንጥፉልኝ አለ” አሉ!)
ይሄኔ ብቻ ነው የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር በኢህአዴግ ጉባኤ ላይ ሊገኝ የሚችለው፡፡ ይሄኔ ብቻ ነው የታሰሩ ፖለቲከኞች በድርድር ሊፈቱ የሚችሉት፡፡ ይሄኔ ብቻ ነው ኢህአዴግና ተቃዋሚዎች በጥላቻ  መተያየታቸውን እርግፍ አድርገው የሚተዉት፡፡ ይሄኔ ብቻ ነው አንዱ ሌላውን ጠልፎ ለመጣል ከማሴር የሚታቀበው፡፡ ይሄኔ ብቻ ነው ተቃዋሚዎች በየሳምንቱ 60 ደቂቃ የቲቪ የአየር ሰዓት ሊመደብላቸው የሚችለው፡፡ ለምን መሰላችሁ? ፖለቲከኞች “የሰይጣን ቁራጭ” የሚሆኑት ሥልጣን ሲኖር ብቻ ነው፡፡ በተረፈ ግን  እንደነሱ መላእክ የለም!
ከምሬ ነው የምላችሁ----ያቺ የህልም ዓለም የምትመስል ኢትዮጵያ የምትፈጠረው ፖለቲከኞቻችን በሂፕኖቴራፒ ሥልጣንን እንዲረሱ ስናደርጋቸው ብቻ ነው፡፡ የፓርቲዎች ዓላማ ሥልጣን መያዝ መሆኑ ጠፍቶኝ እንዳይመስላችሁ ----- ከሥልጣን ጋር እንዲፋቱ “ሂፕኖታይዝድ” ይሁኑ የምለው፡፡ ከሁሉም በፊት ውስጣዊ የስልጣን ጥማት ከሚፈጥረው የአመጻ፣ የፀብ ጫሪነት፣ የጉልበተኝነት፣ የማን አለብኝነት፣ የኢሰብአዊነት … ወዘተ ስሜት መላቀቅ አለባቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ ፍቱኑ መድኀኒት  ሂፕኖሲስ ብቻ ነው፡፡
አይዞአችሁ----ለዝንተ ዓለም ሥልጣንን እንደረሱ አይቀሩም፡፡ ፖለቲከኞች አደብ መግዛታቸውና ሰከን ማለታቸው ከታየ በኋላ በተመሳሳይ የህክምና ዘዴ (Hypnosis) የረሱትን ሥልጣን እንዲያስታውሱ ይደረጋሉ፡፡ (ሂፕኖሲስ የማስረሳትም የማስታወስም አቅም አለው!!)
በነገራችሁ ላይ የዚህ ፕሮፖዛል አላማ እነ አሜሪካ በተፈጥሮአዊ የፖለቲካ ሂደት እውን ያደረጉትን ሥርዓት ለጦቢያ በቴራፒ ማምጣት ነው፡፡ የማታ ማታም ያቺን ህልም የምትመስል ኢትዮጵያ መፍጠር! (“የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው” አሉ!)  እንግዲህ-----ይሄ ፕሮፖዛሌ ተቀባይነት ካገኘ የመጀመሪያ ሥራ መሆን ያለበት (የውጪ ድጋፍ ጠይቀንም ቢሆን!) በርካታ የሂፕኖቴራፒ ባለሙያዎችን በጥራትና በብቃት ማሰልጠን ነው፡፡ ያለበለዚያ ይሄም እንደ እነ ቢፒአር የመክሸፍ  ዕጣ አይቀርለትም (ከመክሸፍም ከማክሸፍም ያውጣን!!)

ሰሞኑን በእጅጉ ማርኮኝ የተመለከትኩት “Trance” የተሰኘ ፊልም ላይ፣ ዋና ገፀ-ባህሪው ሳይመን ሳያውቀው የገባበት የቁማር ጨዋታ (gambling) የለየለት ሱሰኛ ያደርገውና የዕዳ አረንቋ ውስጥ ይዘፈቃል፡፡ ከቁማር ሱሰኝነቱ ለመላቀቅ የዘየደው መላ ወደ ቴራፒስት ዘንድ መሄድ ነው፡፡ በሂፕኖቴራፒ ከቁማርተኝነቱ ለመፈወስ፡፡ ሂፕኖሲስ የህክምናው (ቴራፒው) ሂደት ሲሆን ባለሙያው ወይም ባለሙያዋ ሂፕኖቲስት ይባላሉ፡፡ ቴራፒውን የወሰደው ሰው ደግሞ “ሂፕኖታይዝድ” ሆኗል ይባላል፡፡
በነገራችሁ ላይ ሂፕኖሲስ ታካሚውን በሰመመን ስሜት ውስጥ በማስገባት፣ ሃሳቡንና ትኩረቱን በአንድ የሆነ ጉዳይ ላይ እንዲያነጣጥር፣ የተወሰኑ ቃላትን ወይም ዓ.ነገሮችን በመደጋገም አሊያም የአዕምሮ ምስል በመፍጠር… የሚሰጥ ህክምና (ቴራፒ) ነው፡፡ ሂፕኖሲስ ያልተፈለገ ባህሪን (ድርጊትን) ለማስወገድ ወይም ለመቆ›ጣጠር በቁጥጥር ሥር ለማዋል ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል፡፡ ከሲጋራ ሱሰኝነት ለመላቀቅ፣ ከእንቅልፍ እጦት (Insomnia) ለመገላገል፣ ከመጠን በላይ የመብላት ፍላጐትን ለማስወገድ …ወዘተ ሊያግዝ እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
ወደ ፊልሙ ልመልሳችሁ፡፡ በቁማር ሱሰኝነት ኑሮው የተቃወሰው ሳይመን፤ ኤልዛቤት ላምብ የተባለች ቴራፒስት ዘንድ በመሄድ ችግሩን ተናግሮ ቴራፒውን ይጀምራል፡፡ የቁማር ሱሰኝነቱ ስር የሰደደ በመሆኑ ብዙ ጊዜ እንደሚወስድበት ይገለጽለትና ህክምናውን ይቀጥላል፡፡ በዚህ ሂደትም ከኤልዛቤት ጋር እየተቀራረበ ይመጣል፡፡ የጦፈ የፍቅር ግንኙነትም ይጀምራል፡፡
ቴራፒስቷ ከደንበኞቿ ጋር እንዲህ ያለ ግንኙነት ውስጥ መግባት እንደሌለባት ታውቃለች፡፡ ግን አንዴ ሆነ፡፡ እናም “የፈሰሰ ውሃ አይታፈስም” ብላ ገፋችበት። ከጥቂት ጊዜ በኋላ የሳይመን ፍቅር ወደ ጥርጣሬና ቅናት እየተቀየረ መጣ፡፡ የት ገባሽ፣ የት ወጣሽ ማለት አበዛ፡፡ ፍቅረኛውን የሚያጣት፣ እየመሰለው ይጨነቅ ጀመር፡፡ ቅናቱ እየተባባሰ እንደ እብደት አደረገው፡፡ መላ ህይወቱን እሷ ላይ ጣለ፡፡ ከእሷ ከተለየ የሚሞት ሁሉ መሰለው፡፡ በዚህ የተነሳም ያፈቀራትን ያህል ጠላት፡፡ አንድ ቀን ሬስቶራንት ውስጥ ተቀምጠው ሳለ “ወንድ አየሽ” ብሎ በጥፊ አጠናገራት፡፡ ይሄን ጊዜ ነው ኤልዛቤት ከዚህ ጨዋታ መውጣት እንዳለባት የወሰነችው፡፡ ግን በየት በኩል? ሳይመን አለቅም ብሎ ሙጭጭ አለባት፡፡ ረዥም የይቅርታ ደብዳቤ ፃፈላት። እየደወለ ነዘነዛት፡፡ እያለቀሰ ተማፀናት፡፡ ኤልዛቤት ግን የዚህ መጨረሻ ምን እንደሚሆን አላጣችውም፡፡ ነገርዬው በዚህ ከቀጠለ የማታ ማታ እንደሚገድላት ቅንጣት አልተጠራጠረችም፡፡
ጉዳዩን ለፖሊስ ብታመለክትም ነገሬ ሳይሏት ቀሩ፡፡ ጠበቆች፤ ስሟን ቀይራ አገር ጥላ እንድትወጣ መከሯት፡፡ እሷ ደግሞ ይሄን ለማድረግ ፈቃደኛ አልነበረችም፡፡ ሁለት ጊዜ ተጎጂ መሆንን አልፈቀደችም፡፡ እናም ጉዳዩን በቁጥጥሯ ሥር ለማዋል መረጠች፡፡
ሳይመንን ከቁማር ሱሰኝነት ለመገላገል ወይም ቁማር ለማስረሳት ስትጠቀምበት የቆየችውን ቴራፒ ለዚህ ዓላማ አዋለችው፡፡ “መርሳት የምትፈልገው ቁማሩን ሳይሆን እኔን ነው” በማለት እርሷን እንዲረሳት ተከታታይ ቴራፒ ሰጠችው፡፡ ቀስ በቀስም እሷን እየረሳ መጣ፡፡ እሷን ብቻ ሳይሆን የፍቅር ግንኙነታቸውንም ጭምር ረሳው፡፡ ሁሉ ነገር ከአዕምሮ ትውስታው እልም ብሎ ጠፋ፡፡ የቁማር ሱሱን ሊረሳ ሄዶ ፍቅሩን ረስቶ ተመለሰ፡፡
አንዳንድ በፀብና በቅናት የተሞሉ አደገኛ የፍቅር ግንኙነቶች እንዲህ “ዲሊት” እየተደረጉ ከትውስታ ማህደር ቢጠፉ ብዙ ጥንዶችን ከከፋ ችግር ሊታደጉ ይችላሉ፡፡ በእርግጥ ወደ ፊልሙ መጨረሻ አካባቢ የሳይመን ትውስታ ይመለሳል፡፡ “ለምን እንድረሳ አደረግሽኝ?” ብሎ የቀድሞ ፍቅረኛውን ይጠይቃታል፡፡ ኤልዛቤትም “ትውስታህ በሰረገላ ቁልፍ ተከረቸመ እንጂ ከጥቅም ውጭ አልሆነም” ስትል ትመልስለታለች፡፡
ኤልዛቤት በሂፕኖቴራፒ ክህሎቷ ራሷን ከሞት፣ የቀድሞ ፍቅረኛዋን ደግሞ ከዕድሜ ልክ እስርና ፀፀት ለማትረፍ ችላለች፡፡ ይሄን ፊልም ተመልክቼ ስጨርስ ወደ አዕምሮዬ የመጣው፣ በሃይልና በዱላ የታጀበው የአገራችን የፍቅር ግንኙነት ነው፡፡ በበዛ ቅናት እየተሰቃየ ሚስቱን ለሚደበድብ ባል፤ ይሄ ቴራፒ ግሩም ይመስለኛል፡፡ ፍቅረኛውን ከእነ ትዝታዋ በማስረሳት አዲስ ህይወት እንዲመራ ለማድረግ ይረዳል፡፡
በሂፕኖቴራፒ ሰዎች እንዲረሱ ብቻ ሳይሆን የረሱትንም እንዲያስታውሱ (ትውስታቸው እንዲመለስ) ማድረግ ይቻላል፡፡ ሳይመን ጭንቅላቱ ላይ ጉዳት ከደረሰበት በኋላ ያስቀመጠበት የጠፋበትን የመኪና ቁልፍ በሂፕኖሲስ እንዲያስታውስ አድርጋዋለች - ቴራፒስቷ ኤልዛቤት፡፡ ዓምና ለእይታ የበቃውን “Trance” የተሰኘ ፊልም ፈልጋችሁ ተመልከቱት፡፡ ድንቅ ፊልም ነው!! (በነገራችሁ ላይ እኔ የተረኩት ከሙሉ ፊልሙ እጅግ ጥቂቱን ብቻ ነው)

ባለፈው ሳምንት በጎንደር የቅማንቶች መብት ተሟጋች ከሆኑት ከአቶ ነጋ ጌጤ ጋር ባደረግነው ቃለ-ምልልስ “ጎንደር የቅማንቶች ናት” በማለት ሰፊ ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡ ዛሬ ደግሞ የታሪክ ተመራማሪው አቶ ሲሳይ ሳህሌ በጎንደር ታሪክና ሥልጣኔ ዙሪያ የሰጡንን ማብራሪያ እናቀርባለን፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ ቃለ-ምልልስ ያደረገላቸው የታሪክ ተመራማሪ፣ የፈረንሳይ ከተማ “ቬንሰንት - ጎንደር ያልተማከለ የትብብር ስምምነት የራስ ግንብ ሙዚየም ፕሮጀክት አስተባባሪም ናቸው፡፡

 ጎንደር እንዴት ተመሰረተች?
በ1623 ሰኔ ወር ላይ አፄ ሱንስዮስ ለልጃቸው ለአፄ ፋሲል በህይወት እያሉ ስልጣናቸውን ያስተላልፋሉ፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ሜንዴዝ የሚባል የካቶሊክ ሚሽነሪ መጥቶ ነበር፡፡ አዘዞ (አሁን አፄ ቴዎድሮስ ኤርፖርት ያለበት ቦታ)፣ ጎርጎራ እና ደንቀዝ የሚባሉ ቦታዎች ሶስት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያኖች ተሰርተው ነበር፡፡ ደንቀዝ ላይ ያለው እንደ ቤተመንግስትም ያገለግል ነበር፡፡ አፄ ሱስንዮስ ስልጣናቸውን አስተላልፈው ያረፉትም በዚሁ የካቶሊክ ደብር ውስጥ ሆነው ነው፡፡ ከዚያ በኋላ አፄ ፋሲለደስ የህዝቡን ፍቃድ ለማሟላት ኢየሱሳውያኑን ከሃገር አባረሩ፡፡ ስልጣናቸውን ተቀብለው አፄ ከተባሉ ከ4 ዓመታት በኋላ አሁን ቤተመንግስታቸው ከሚገኝበት ቦታ መጥተው የዛሬዋን ጎንደር ሊመሰርቱ ችለዋል፡፡
ለምን ወደ ጎንደር መምጣት አስፈለጋቸው? እዚያው አባታቸው የነበሩበት ቦታ ላይ መንግስታቸውን መመስረት አይችሉም ነበር?
በሶስት ምክንያቶች ነው እንደዚያ ያደረጉት። አንደኛው ከእምነት አንፃር፣ ጎርጎራ ካቶሊካውያኑ የነበሩበት ቦታ ስለነበር የረከሰ ነው ተብሎ ታመነ። ስለዚህ አዲስ ቦታ መቀየር አስፈለጋቸው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት፣ ጎርጎራ ወባማ አካባቢ ስለነበር ሰራዊታቸውን ፈጀባቸው፡፡ እናም ከጤና አኳያ የአሁኑ ጎንደር ተመራጭ ሆነ፡፡ ሦስተኛው ምክንያት፣ ጎንደር ወይና ደጋ አየር ንብረትና ከ40 በላይ ምንጮች ያላት ነበረች፡፡ በወንዞችም የተከበበች በመሆኗም የሰራዊቱን የውሃ ፍላጎት ታሟላ ነበር፡፡
አሁን ቤተ መንግስቱ ያለበት ቦታ 2200 ሜትር ከባህር ጠለል በላይ ከፍታ አለው፡፡ ዙሪያውን ደግሞ እስከ 3 ሺህ ሜትር ከፍታ ያላቸው ተራራዎች አሉ። እነዚህ ተራራዎች የአየር ወለድ በሽታ ቢመጣ ወደ ከተማዋ አያስገቡም/አያሳልፉም ተብሎ ይታሰባል፡፡ ከጦር ስትራቴጂ አንፃርም በተራራ መከበቧ ጠላት በቀላሉ እንዳይገባ ይከላከላል፡፡ ተራራዎቹ በትልልቅ ዛፎች የተጠቀጠቁ መሆናቸውም የማገዶ ፍጆታን ያሟላሉ፡፡ በእነዚህና በሌሎች ምክንቶች ጎንደር በ1628 ዓ.ም ተመሰረተች፡፡
አፄ ፋሲለደስ በ1660 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ፣ የጎንደር ህዝብ ብዛት 27 ሺህ ደርሶ ነበር። ይሄ የሚያሳየው ከተማዋ በወቅቱ እጅግ ሰፊ መሆኗን ነው፡፡ በእነ እቴጌ ምን ትዋብ ዘመን ደግሞ የህዝብ ብዛቱ እስከ 100 ሺህ ደርሶ ነበር፡፡
ከብሄር፣ ከሃይማኖት አንፃር ምን አይነት ማህበረሰብ ነበር የሚኖርባት?
እንደውም ጎንደርን በወቅቱ ከነበሩት የሃገሪቱ አካባቢዎች ለየት የሚያደርጋት ቤተ እስራኤሎች፣ ባህላዊ እምነት ተከታዮች፣ ሙስሊሞች፣ የውጭ ዝርያ ያላቸው ቱርኮች… ሁሉም አንድ ላይ እንደልባቸው ተስማምተው የሚኖሩባት መሆኑ ነበር፡፡ በተለያዩ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ የህብረተሰብ ክፍሎችም ይኖሩባት ነበር፡፡ አናፂዎች፣ ግንበኞቹ፣ ሸማ ሰሪዎች፣ የብረታ ብረትና የወርቅ ስራ የሚሰሩ እንዲሁም ነጋዴዎች ሁሉ አንድ ላይ ይኖሩባት ነበር፡፡ በጊዜው ንግዱን በሚገባ ያውቁታል ተብሎ ስለሚታመን ነጋድራሶች ከሙስሊሞች ነበር የሚመረጡት፡፡
አፄ ፋሲለደስ ቤተ-መንግስታቸውን ካሳነፁ በኋላ በዙሪያው ሰባት ቤተ-ክርስቲያኖችን አሰርተዋል፡፡ በየጊዜው ነገስታቱ እየተተኩ ለ120 ዓመታት እጅግ የረቀቀ የህንፃ ግንባታ ጥበብን ሰርተው አልፈዋል፡፡ የጎንደር ስልጣኔ የመጨረሻዋ ንግስት የነበሩት እቴጌ ምንትዋብም የራሳቸውን ቤተ-መንግስትና ቤተ-ክርስቲያን አሳንፀዋል ቁስቋም ትባላለች፡፡
አፄ ፋሲል ለምን 7 ቤተ-ክርስቲያናትን በዙሪያቸው አሰሩ?
በወቅቱ እንደሚታወቀው ነገስታቱ በእምነታቸው ጠንካሮች ነበሩ፡፡ የጊዮርጊስ ታቦት ዘማች ታቦት ነው፤ ተዋጊ ነው፡፡ በአድዋ ጦርነት ጊዜም ቢሆን አፄ ምኒልክ ይዘው ዘምተዋል። የድንግል ማርያም ደግሞ ከንግስቲቱ ማረፊያ ቤት አጠገብ እንድትተከል ተደርጓል፡፡ ከትውፊቱ ከተቀበልነው ታሪክ እንደምንረዳው፣ አፄ ፋሲል ቤተ መንግስታቸውን ሲገነቡ አውሬ ሲያስቸግራቸው ባህታውያን የአቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስን ታቦትን ትከል ብለው ሲመክሯቸው ያንን አደረጉ፡፡ መብረቅ ሲያስቸግራቸው የቅዱስ ሚካኤልን ታቦት፣ በሽታ ሲያስቸግራቸው የዓለም መድኀኒት የሆነውን የመድኀኒዓለም ታቦት እንዲተክሉ ተመከሩ፡፡ በዚህ ሂደት ነው ደብራቱን በዙሪያቸው የተከሉት ተብሎ ይነገራል፡፡ በሌላ በኩል በወቅቱ ካቶሊኮች ተባረው “ፋሲል ይንገስ ሃይማኖት ይመለስ” ተብሎ ሲታወጅ፣ አፄው ለሃይማኖታቸው ያላቸውን ፅናት ለማሳየት በርካታ ቤተ-ክርስቲያናትን እንደተከሉ ይታመናል፡፡
በዚያን ጊዜ የቤተ-መንግስቱ የአኗኗር ስርአት ምን ይመስል ነበር?
በአጠቃላይ የቤተ መንግስቱ ቅጥር ግቢ 70 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ነው ያረፈው፡፡ 12 በሮችም አሉት፡፡ ወደ ቅፅሩ የሚገባው እንደየደረጃውና ማዕረጉ በሚፈቅድለት በር ብቻ ነው፡፡ ራስች በር - ራሶች ብቻ የሚገቡበት ነው፣ የንጉሱ በር (ጃንተከል በር) ንጉሱ ብቻ የሚገቡበት ነው፡፡ ግምጃ ቤት በር የሚባል አለ - የግምጃ ቤት አስተናባሪዎች የሚገቡበት ነው፡፡ ቀጭን አሸዋ በር የሚባል አለ ይህ የግንባታ እቃዎች የሚገቡበት በር ብቻ ነው፡፡ እርግብ በር የሚባለው ደግሞ የደናግላን እና የመነኮሳት በር ነው፡፡ እንቢልታ ነፊዎች ብቻ የሚገቡበት ደግሞ እንቢልታ በር ይባላል፡፡ በሃዘን ጊዜ ሃዘንተኞች የሚገቡበት በር ተዝካሮ በር ይባላል፡፡ ተዝካሮ በር ፊት ከቤተመንግስቱ በስተደቡብ ባለው አነስተኛ ሜዳ ላይ አስከሬን ተቀምጦ ይለቀሳል፡፡ በጥንቱ የጎንደር ባህል ቦታው ሰዎች ሲሞቱ አስከሬናቸው ተቀምጦ ረዘም ላለ ሰአት ለቅሶና የሽኝት ስነ ስርዓት የሚከወንበት ነው፡፡ ባልደራስ በር የሚባለው ደግሞ ፈረሰኞችና የፈረሰኛ አዛዥ በር ነው፡፡ የንጉሱ ፕሮቶኮሎች የሚገቡበት በር ደግሞ “ኳሊ” በር ይባላል፡፡ በዚህ በኩል ባለጉዳዮችም ሆኑ የንጉሱ የቅርብ አጋዞች ይስተናገዱ ነበር፡፡
ንጉሡ በወቅቱ የከተማውን ህዝብ ግብር ያበሉ ነበር?
እንግዲህ በኢትዮጵያ ታሪክ ንጉሱ ግብር ካላበላ ምኑን ንጉስ ሆነው ይባል ነበር፡፡ ግብር ማስገበርም አለበት፡፡ ግብር በወርቅ፣ በብር፣ በከብት፣ በአሞሌ፣ በጥይት በመሳሰሉት መልክ ከነዋሪው ይሰበሰባል። ንጉሱ ደግሞ በምትኩ ለታችኛው የህብረተሰብ ክፍል ግብር ሰብስቦ በየጊዜው ያበላል፡፡ ራሶችና መኳንንቶችም በየአውራጃቸው ላለ ህዝብ ግብር ማብላት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ግብር ሲበላ ሰው እንደማዕረጉ ነው የሚቀመጠው፡፡ መጀመሪያ ንጉሱ ይቀመጣሉ፤ ከዚያ ንግስቲቷ ይቀጥላሉ፣ እጨጌውና የአክሱም ንቡረ ዕድ ይከተላሉ፡፡ እንዲህ እንዲያ እያለ መኳንንቱ በየደረጃቸው ይቀመጣሉ፡፡ ብዙውን ጊዜ ከፋሲካ በኋላ ነው ግብር የሚበላው፤ በበአላትም እንደአስፈላጊነቱ ንጉሱ ደግሶ ህዝቡን ያበላል፡፡  
ዳኝነት እና ፍርድስ እንዴት ነበር የሚከናወነው?
ዳኝነት እሚሰጠው እምነትን መሰረት በማድረግ ነበር፡፡ የእምነት ወይም ከፍተኛ ሃገራዊ ጉዳይ ከሆነና በመኳንንቱ መወሰን የማይችል ከሆነም ዙፋን ችሎት ላይ ይቀርባል፡፡ በእምነት ጉዳይ ክርክር ስለመካሄዱ ሁሌም በምሳሌነት የሚጠቀሰው የአልፈንዞ ሜንዴዝ እና የእጨጌ ጊዮርጊስ ክርክር ነው፡፡ በወቅቱ አልፈንዞ ሜንዴስ ከእጨጌው የሚቀርብለትን መከራከሪያ መመለስ አቅቶት ነበርና አንድ ጥያቄ ጠየቃቸው። “ስላሴዎች ሁል ጊዜ ፀጉራቸውን የማይላጩት ለምንድን ነው?” በማለት እሳቸውም “አንተ ቅንድብህን ትላጨዋለህን?” ሲሉ ጥያቄውን በጥያቄ መለሱለት፡፡ ቀጥሎም “የአብ ፊቱ ወዴት ነው?” ሲል ጠየቀ፡፡ እሳቸውም ጧፍ አበሩና “የዚህ መብራት ፊቱ ወዴት ነው?” አሉት፡፡ መልስ ሊሰጣቸው አልቻለም፡፡ በዚህም የእግዚአብሔር ፊት በሁሉም አቅጣጫ ነው ብለው ክርክሩን ረቱት ይባላል፡፡
ከፋሲል በኋላ አፄ (ፃድቁ) ዮሐንስ ነበሩ፡፡ እሳቸው የእንስሳትን መብት እስከማስጠበቅ የደረሱ ሰው ናቸው፡፡ ከደግነታቸው ብዛት ትልቅ ደውል በውጨ በኩል አስተክለው ነበር፡፡ ዳኝነት ጎደለብኝ ተበደልኩ የሚል ሰው መጥቶ ይደውላል፡፡ ከዚያም ይገባና ከንጉሱ ዘንድ ፍርድ አግኝቶ ይሄዳል፡፡ አንድ ጊዜ ምን ሆነ፡- ዝናብ እየዘነበ ነበር፡፡ ደውሉ ይደወላል፡፡ በዚህ ዝናብ ማን ፍርድ የጎደለበት ይሆን የመጣው ብለው እልፍኝ አስከልካያቸውን ይልኩታል፡፡ “ኧረ ጃንሆይ  አህያ ነው እንጂ ሰውስ የለም” ይላቸዋል፡፡ አህያውን አስገባው አሉት፡፡ አህያው ሲታይ ጀርባው ተጋግጧል፡፡ ባለቤቱ ተፈልጎ ይቅረብ ተባለና መጣ፡፡ “ለምን እንዲህ አደረክ፣ እድሜ ልኩን ያገለገለህን አህያህን ለምን ጣልከው?” ሲሉ ሰውየውን ገስጸው ቀጥተው ላኩት፡፡ አህያው ደግሞ በቤተ መንግስት ውስጥ ገብስና ባቄላ እየበላ እንዲኖርና ከቁስሉ እንዲያገግም ተደረገ፡፡ በዚያውም “የተገጠበ አህያ ጭነት እንዳይጫን” የሚለው አዋጅ ታወጀ፤ ጭኖ የተገኘም ይቀጣ ነበር፡፡ ያኔ ነው የእንስሳት መብት የታወጀው፡፡
ጎንደር የ44 ታቦታት መገኛ ሲባል ምን ማለት ነው?
ጎንደር ከመመስረቷ በፊት በአካባቢው አራት ደብሮች ነበሩ፡፡ አንደኛው አርባዕቱ እንስሣ ይባላል፡፡ በሌላ አቅጣጫ ቃአ ኢየሱስ የሚባል አለ፡፡ ጊዮርጊስ በሌላ አቅጣጫ አለ፤ አበራ ጊዮርጊስ የሚባልም አለ። ከዚያ በኋላ አፄ ፋሲል 7 ተከሉ፡፡ ፃድቁ ዮሐንስ 2 ተከሉ፣ አድያም ሰገድ ኢያሱ ደብረ ብርሃን ስላሴ ጨምሮ 2 ተከሉ፡፡ እንዲህ እንዲያ እያሉ ነገስታቱ በተፈራረቁ ቁጥር አዳዲስ ደብሮችን ሲተክሉ ኖሩ። በዚህ ሂደት በእነዚህ ነገስታት 30 ተተከሉ። 14 ያህሉ ደግሞ ቀድሞም የነበሩ ናቸው፡፡ እነዚህ ተደምረው ጎንደር የ44 ታቦት መገኛ ሃገር ተባለች፡፡ ኋላ ላይ በደርቡሽ ጦርነት 4 ያህሉ ተቃጥለው ነበር፡፡ ሃገሬው የተቃጠሉትን እንደገና ሰርቷቸው ነበር፡፡ አሁን ሁለቱ እየተሰሩ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ሌሎች ደብሮች በብዛት የተተከሉ ቢሆንም የጥንቱን የጎንደር ስልጣኔ ለማስታወስ 44ቱ ታቦታት የጎላ ቦታ አላቸው፡፡
ጎንደር የሚለው ስያሜስ ከየት የመጣ ነው?
ብዙ አፈታሪኮች አሉ፣ ነገር ግን ዋናው ማየት ያለብን የታሪክ ጥራዞችን ነው፡፡ የአፄ አምደፅዮን ዜና መዋዕል ላይ “ጎንደር” የሚለው ስም ሰፍሯል። ጎንደር ከመመስረቷ ከ300 ዓመት በፊት መሆኑ ነው፡፡ ወደ አፈታሪኩ ስንመለስ ቃሉ የማን እንደሆነ ባይታወቅም ጉንዳ ሃገር ወይም ትልቅ ሃገር ማለት ነው፡፡ አንዳንዶቹ ጓንግ እና ዳራ ከሚሉ ሁለት ቃላት የመጣ ሲሆን በአንገረብ እና ቃሃ ወንዝ መካከል ስላለች ነው ይህ ስም የተሰጣት ይላሉ፡፡ ግን የተጨበጠ ነገር የለውም፡፡
ነገስታቱ ይህን የቤተመንግስቱን ቦታ ከመያዛቸው በፊት ቦታው ላይ ምን ነበር?
እንደ አፈታሪክ እዚህ ቦታ ላይ (አሁን ቤተመንግስቱ ያለበት) ውሃ ነበር ይባላል፡፡ ውሃውን አድርቀው ቤተ መንግስታቸውን ሰሩ፤ አንዳንድ ታሪክ ደግሞ ቦታው የባላባቶች/የእርሻ ቦታ ነበር ይላሉ። ሌሎች አፈታሪኮች አፄ ፋሲል አደን ወጥተው አንዳንዶች ጎሽ ይላሉ ሌላው አንበሳ ይላል እያባረሩ መጥተው እዚህ ቦታ ሲደርሱ ተሰወረባቸው፤ ባህታዊ ተገልጦ ቤተ መንግስትህን የምትሰራበት ቦታ ይሄ ነው ብሎ ነገራቸው ይባላል፡፡ ከዚያ በፊት መላዕኩ ራጉኤል “ጎ” የሚባል ቦታ ላይ ትነግሳለህ ብሎ በራዕይ ይነግራቸው እንደነበር ይነገራል፡፡ “ጎ” ሲላቸው ቦታውን ፍለጋ ጎዛራ፣ ጎጃም፣ ጎርጎራ ሄደው በመጨረሻ ጎንደር ፀንቶላቸዋል ነው የሚባለው። ነገር ግን በዚህ አካባቢ አድባራት በፊትም መኖራቸውን ስናይ ሰዎች ይኖሩበት እንደነበር ያመላክተናል፡፡
የኖህ መቃብር ነው የሚል ታሪክም ይነገራል?
ሰዎች የራሳቸውን ታሪክ ይዘው ሊነሱ ይችላሉ። እኔም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይሄን ነገር ሰእየሰማሁ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በ1960ዎቹ የተፃፈ አንድ ታሪክ የሚያሳየው፤ ፋሲል ቤተመንግስቱን እንደ ኖህ መርከብ አድርጎ እንደሰራው ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው ታሪክ የመጣው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው፤ ግን ሰፊና ጥልቀት ያለው ጥናት ይፈልጋል፡፡
በ150 ዓመታቱ የጎንደር ስልጣኔ ከታዩ ዘመናዊ ነገሮች ጥቂቶቹን ቢጠቅሱልን…
የቤተ መንግስቱ የህንፃ ጥበብ ዋናው ነው፡፡ አንዳንዶች የውጭ ሰዎች እጅ አለበት ይላሉ፤ ነገር ግን አሰራሩ በፊትም በአክሱም ዘመነ መንግስት የነበረ ነው፡፡ ህንዳውያንም ሆነ ፓርቹጋሎች ከመምጣታቸው በፊት እንደነበር ይናገራል፡፡ እ.ኤ.አ ከ1563-97 ዓ.ም የነገሱት አፄ ሰርፀድንግል ቤተ መንግስታቸው እንፈራዜ የምትባል ቦታ (ከጎንደር ወደ ባህርዳር ሲሄድ 60 ከሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ቦታ) ላይ የሚገኝ ቤተ መንግስት ላይ ይህ ቴክኖሎጂ ተሰርቶበታል፡፡ ስለዚህ የውጭ ኃይሎች እጅ አለበት የተባለው አያሳምንም፡፡
ሌላው ግዙፍ የሆኑ የንግድ መስመሮች - እስከ አውሮፓ፣ ኤሽያ የሚዘልቁ ተፈጥረው ነበር፡፡ የቤተ መንግስቱን አኗኗር ካየን ደግሞ ዘመናዊ ነበር፡፡ ዛሬ ፋሽን የምንለው… በዚያን ጊዜ ቀጭን ፈታዮች በሚባሉ ባለሙያዎች ለቤተ መንግስቱ ወይዛዝርት በየአይነቱ አልባሳት እየተሰሩ ያንን ፋሽን ይከተሉ ነበር፡፡ ዛሬ “ስቲም” የምንለው ያኔ “ወሸባ” ይባል ነበር፡፡ የፀጉር፣ የንቅሳት አይነት እንደፋሽን ይታይ ነበር፡፡ ዛሬ ዶሮ አስራ ሁለት ብልት አላት እንላለን። ያ መለኪያ የወጣው በወ/ሮ ምንትዋብ ጊዜ ነው። የዓሣ አሰራርና የተለያዩ የምግብ አሰራሮች ያኔ የመጡ ናቸው፡፡ ይህ ስርአት እንግዲህ ወደ ከተማው ተስፋፍቷል፡፡ እኛ ዛሬ የተጣራ ውሃ እያልን የታሸገ ውሃ እንጠጣለን፡፡ ይሄ በዚያን ጊዜም ይደረግ ነበር። የፈረስ ማቆሚያ (ፓርኪንግ) አገልግሎት ይሰጥ ነበር፡፡ ዛሬ የመኪና ፓርኪንግ እንደምንለው በአፄ በከፋ ዘመን ባለ ዘጠኝ በር ዘመናዊ የፈረስ ማቆሚያ /ፓርኪንግ/ ተሰርቶ ነበር፡፡ እንግዶች ፈረሶቻቸውን እዚያ ነበር የሚያቆሙት፡፡
በ5 ዓመት የጣሊያን ወረራ ቤተ መንግስቱ ለጣሊያን ገዢዎች መቀመጫነት አገልግሏል ይባላል?   
በሚገባ አገልግሏል፡፡ እንዲያውም ጣሊያን ከተማዋን ለሁለት ከፍሎ ነበር የሚያስተዳድረው። ከጃን ተከል በታች ያለው የሃገሬው ወይም የሃበሻ መንደር ነበር፡፡ አሁን ፒያሳ የምንለው ደግሞ የጣሊያኖች ነበር፡፡ ያኔ ሃበሾች ወደ ነጮች መንደር መዝለቅ አይፈቀድላቸውም፡፡ በቤተ መንግስቱ ውስጥም ለግብር በሚቀመጡበት ወቅት ነጮቹ በተመረጠ ቦታ ሃገሬው በሌላ ቦታ ሳይቀላቀሉ እንዲቀመጡ ይደረጋል፡፡ ምግብ ሲቀርብም ነጮቹ በስርአቱ ይመገባሉ፡፡ ሃበሾቹ ተሻምተው እንዲመገቡ ይደረግ ነበር፡፡ ጣሊያን ቤተ መንግስታቱ በጥቁሮች መሰራታቸውን አምኖ ላለመቀበል “የፖርቹጋል ግንቦች” ይላቸው ነበር፡፡ የከተማዋን ስያሜዎችም በብዛት ቀይሮ ነበር፡፡
ጃንተከል ዋርካ ዝነኛ ነው፤ ስለሱ ታሪክ ይንገሩን…
ጃንተከል እንግዲህ አፄ ፋሲል ተከሉት ተብሎ ይታመናል፡፡ ለዚያም ነው ጃንሆይ የተከሉት ለማለት ጃን ተከል የተባለው፡፡ በወቅቱ የሃገር ሽማግሌዎች በስሩ ተቀምጠው ይወያዩ ነበር፡፡ ስቅላትን የመሳሰሉ ፍርዶችም ይፈፀሙበት እንደነበር በስፋት ይነገራል።

Published in ባህል

ከ“አነስተኛና ጥቃቅን” ተነስቶ፤ ዛሬ የአለማችን ባለ ሃብት ሆኗል!
እንደ ቻይና ወጣቶች በቢል ጌትስ የቢዝነስ አርአያነት ለብልጽግና እንጥራለን?
ወይስ እንደ ለማኝ በቢል ጌትስ ምጽዋት ተማምነን እጅ እንስማለን?

“የአገሬ ሰውና የአገሬ መንግስት ይመሳሰላሉ፤ ራሳቸውን ጠልፈው መጣል ይቀናቸዋል” በሚል ርዕስ ባለፈው ሳምንት በአዲስ አድማስ የወጣው ጽሑፍ፤ በአንድ ሃሳብ ላይ የሚያጠነጥን ነበር። ስለ እድገትና ብልጽግና እናወራለን፡፡ ጥሩ ነገር መመኘት በጐ ነው፡፡ ነገር ግን ምኞታችንን እውን እንዳናደርግ፤ ራሳችንን ጠልፈን እንጥላለን ይላል ጽሑፉ፡፡ እንዴት?
ብልጽግናን፣ ቢዝነስን፣ ስኬታማንና ትርፋማነትን ከማክበር ይልቅ “የዚህ አለምን ህይወት” እየናቅን፤ መመነንን፣ ችግር መካፈልን፣ ምጽዋትን፣ ምስኪንነትንና መስዋዕትነትን እናመልካለን፡፡
በአንድ በኩል ብልጽግናን ብንመኝም፤ በሌላ በኩል ሁለመናችንን በፀረ ብልጽግና ሃሳቦችና ባህሎች ተብትበን አስረነዋል፡፡ እንዲህ ራሳችንን ጠልፈን የመጣል አባዜ እንደተጠናወተን የሚገልፀው ጽሑፍ፤ በርካታ ሰሞነኛ ዜናዎችን በማስረጃነት ያቀርባል፡፡ ይህ የምዕተ ዓመታት “በሽታ” ምንኛ ስር የሰደደና በሰፊው የተንሰራፋ እንደሆነም በዝርዝር ያስረዳል፡፡ እውነትም የባህል እና የአስተሳሰብ “በሽታ” ተጠናውቶናል፡፡ ሃሙስ እለት በቢል ጌትስ “የክብር ዶክትሬት” ሽልማት ላይም በግላጭ አየሁት - “የቢዝነስ ስኬትህን ሳይሆን የምጽዋት እጅህን እናደንቃለን” ብለን ሸለምነው፡፡
ይሄ ነው ዋናው በሽታችን - ለኋላቀርነትና ለድህነት የዳረገን ነባር በሽታ! በእርግጥ አንዳንድ ሰዎች በሽልማቱ ዙሪያ ሌላ ሌላ ቅሬታ ሲያነሱ ሰምቻለሁ፡፡ ለምሳሌ፤ የስራ ባልደረባው በማኔጅመንት መስክ ትምህርቱን ተከታትሎና ጥናት አካሂዶ በዶክትሬት ዲግሪ እንደሚመረቅ የገለፀልኝ አንድ ባለሙያ፤ የዚህኛው ዶክትሬት “የክብር ዶክትሬት” አይደለም ወይ? ሲል ጠይቋል። በእርግጥም የትምህርት ተቋም ውስጥ ገብቶ፤ በዶክትሬት ዲግሪ መመረቅ…ማለትም በማንኛውም መስክ የእውቀትና የክህሎት፣ የአቅምና የብቃት ባለቤት ወይም ጌታ መሆን፣ ትልቅ “ክብር” ነው፡፡
በዚያው መጠን፤ ከትምህርት ተቋም ውጭም፤ ብቃቱን ተጠቅሞ የስኬትና የሃብት ባለቤት (ጌታ) ለመሆን የቻለም፤ ክብር ይገባዋል፡፡ ደግሞስ ሌላ ምን የክብር ምንጭ አለ? የአንዳች ጠቃሚ ነገር ባለቤት፣ ጌታ ከመሆን ውጭ ሌላ የክብር ምንጭ የለም፡፡ ከሺ ዓመታት በፊት በስልጣኔ ጐዳና ሲራመዱ የነበሩት ኢትዮጵያውያን፣ ይህ እውነት ገብቷቸው ነበር፡፡ “ባለ” ወይም “በዓለ” የሚሉ ቃላት በመጠቀም ነበር አክብሮትና አድናቆታቸውን የሚገልፁት - ዛሬ “ባለ ሀብት” እንደምንለው፡፡
“ባለ” ወይም “በዓለ”… የአንዳች ነገር ባለቤት ወይም ጌታ መሆንን - ያስገነዝባል፡፡ ከዚህም ጋር ክብርና አድናቆትን ይገልፃል፡፡ በዓል ማለት ጌትነትና ባለቤት ነው፤ ክብር እና ሞገስም ነው፡፡ ለአማልክት እና ለጀግኖች፤ “በዓል” የሚል የማዕረግ መጠሪያ ይጠቀሙ ነበር፡፡ ባለነበል (ነበል -ባል)፤ የእሳት ጌታ ነው እንደማለት፡፡ ባለሀብት፣ ባለአገር፣ ባለአምባ ወዘተ… ብቃትና ባለቤትነትን፣ ከጀግንነትና ከክብር ጋር አጣምረው ነበር የሚያስቡት፡፡ ቅዱስ ሲሉ ጀግና ማለታቸው ነበር፡፡
ከጊዜ በኋላ የስልጣኔ አስተሳሰብ ሲጠፋ የስልጣኔ ጉዞውም ተረሳ፡፡ “የዚህ አለም ነገር” ሁሉ ከንቱ ነው ተባለ፡፡ የእውቀትም ሆነ የብቃት፣ የስኬትም ሆነ የሃብት ባለቤትነት ተናቀ፡፡ ክብርም አጣ፡፡ በዚያው መጠን ድንቁርናና ምስኪንነት፣ ውድቀትና ድህነት የሚወደስበት ኋላቀር ባህል ወረስን፡፡ እናም፤ ስልጣኔንና ብልጽግናን የምንፈልግ ከሆነ፤ በትምህርት ተቋምም ሆነ በሌላው የህይወት አለም የብቃትና የስኬት ባለቤትነትን ማክበር ይገባል፡፡ ለቢል ጌትስ የተዘጋጀው “የክብር ዶክትሬት” በዓይነቱ በአፍሪካ የመጀመሪያው ነው መባሉ ያልተዋጠላቸው ሰዎች በበኩላቸው፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ብቻ ሳይሆን መንግስት ጭምር የገባበት ጉዳይ መሆኑ እንደ ትልቅ ነገር መቆጠር የለበትም ብለዋል፡፡
ለተራ ነገርና ለቁም ነገር፣ ለትንሹም ለትልቁም… እንዲያው በዘፈቀደ “በአፍሪካ የመጀመሪያው…” እየተባለ ሲነገር መስማት ሊያስጠላ ይችላል፡፡ የአዲስ አበባ አስተዳደር፤ የጐዳና ቆሻሻ የሚያፀዱ መኪኖችን እንደሚገዛ የገለፀ ሰሞን፤ “በአፍሪካ ደረጃ በሁለተኝነት የሚጠቀስ” ማለቱን ታስታውሱ ይሆናል፡፡
እንግዲህ ነገሩን ስታስቡት፤ “በአፍሪካ የመጀመርያው፣ በአፍሪካ ሁለተኛው…” የሚያስብል ጉዳይ አይደለም፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ መረጃው እውነት ነው፡፡ ከ20 ዓመታት በፊት እዚሁ አገራችን ውስጥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጐዳና ማጽጃ መኪና ይጠቀም ነበር፡፡ በበርካታ የአፍሪካ አገራትም እንዲሁ ከአመታት በፊት ተጀምሯል፡፡ ይህንን መረጃ ለማግኘት፤ በኢንተርኔት አንድ ሁለት ደቂቃ ድረገፆችን ገለጥለጥ ማድረግ ይበቃል፡፡ ዛሬ‘ኮ …ክብር ለነ ቢል ጌትስ ይድረሳቸውና፤ ጀግኖቹ የቴክኖሎጂና የቢዝነስ ሰዎች በየበኩላቸው በተቀዳጁት የጥረት ስኬት አማካኝነት፤ እንደ “ተዓምር” በሚያስደንቅ ሁኔታ በቀላሉ ብዙ ብዙ መረጃ ማግኘት የምንችል ሰዎች ሆነናል፡፡ የብቃት ባለቤት አድርገውናል - የብቃት ባለቤት የሆኑ ጀግኖች፡፡
ለማንኛውም ለቢል ጌትስ የተሰጠ የክብር ዶክትሬት…”በዩኒቨርስቲ ብቻ ሳይሆን በመንግስትም ጭምር የተዘጋጀ ስለሆነ ከአፍሪካ የመጀመሪያው ነው” መባሉ ብዙም ትርጉም የለውም፡፡ “ከአፍሪካ የመጀመሪያው” የሚል ተቀጥላ ሳያስፈልገው፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ መንግስት ለቢል ጌትስ ክብር እና አድናቆቱን ገለፀ ቢባል በቂ ነው፡፡ እንዲያውም “ትልቅ ቁም ነገር” ሊሆን ይችል ነበር፡፡ ለምን በሉ፡፡
ብዙዎቻችን ብልጽግናን እየተመኘን የስኬትን ወሬ ማዘውተር ጀምረን የለ? በጐ ጅምር ነው። መንግስትም እንዲሁ ስለ እድገትና ብልጽግና እየደጋገመ ማውራቱ መልካም ነው፡፡ “ዋናው ጠላታችን ድህነት ነው” በሚል አባባል የሚታጀበው የመንግስት ንግግር፤ የአገሪቱ የወደፊት ተስፋ ያለው “ሃብት ፈጣሪ የኢንዱስትሪ ቢዝነስ” ላይ እንደሆነ ይገልፃል፡፡
ሃብት ፈጣሪ የኢንዱስትሪ ቢዝነስ የሚስፋፋው እንዴት ነው? ብላችሁ ጠይቁት፡፡ ምላሽ ይሰጣችኋል፡፡ የመንግስት የኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ፣ የአምስት አመት የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ፣ አመታዊ የኢኮኖሚ ሪፖርት…እና ሌሎች ሰነዶችን ስትመለከቱ፤ ተመሳሳይ ምላሽ ታገኛላችሁ፡፡
ከድህነት በመላቀቅ ብልጽግናን እውን የምናደርገው፤ ሃብት ፈጣሪ የቢዝነስ ሰዎች ሲበራከቱ ብቻ እንደሆነ የሚገልፀው መንግስት፤ የተማሩ ወጣቶች በሥራ ፈጣሪነት በአነስተኛና ጥቃቅን የቢዝነስ መስክ እየተሰማሩ ስኬታማ ሲሆኑ፤ ትልልቅ የኢንዱስትሪ ቢዝነስ እንደሚስፋፋ ያስረዳል፡፡ በዚህም ምክንያት “የኢንተርፕርነርሺፕ አስተሳሰብ፣ እውቀትና ክህሎት” ቀዳሚ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል” ሲልም በሰነዶቹ ይገልፃል - ለአገሪቱ የብልጽግና ተስፋ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን በመጥቀስ፡፡ በአጭሩ፤ ከችጋር ሳንላቀቅ በህይወት ለመቆየት ብቻ የምንፈልግ ከሆነ እርዳታና ምጽዋት ላይ ማተኮር እንችላለን፡፡ ድህነትን ወዲያ አሽቀንጥረን ወደ ብልጽግና ለመንደርደር ከፈለግን ግን፤ በአነስተኛና ጥቃቅን ቢዝነስ ላይ ተሰማርተው ለብልጽግና የሚጣጣሩ ሚሊዮን ወጣቶች፣ ስኬታማ ሃብት ፈጣሪዎች፣ ትርፋማ የቢዝነስ ሰዎች ያስፈልጉናል ይላል መንግስት፡፡
ታዲያ ሃብት ፈጣሪ ይሆናሉ ተብለው ለሚጠበቁ ለእነዚህ ወጣቶች፣ ከእነቢል ጌትስ የበለጠ አርአያና ጀግና ከወዴት ይገኛል? እንደ አብዛኛው አነስተኛና ጥቃቅን ተቋም፤ ቢል ጌትስ ከቤተሰቦቹ መኖሪያ ቤት ስር፣ ጠባብ ምድር ቤት ውስጥ ነው ቢዝነሱን የጀመረው፡፡ በአካባቢው ለሚገኙ ትናንሽ ድርጅቶች አነስተኛ አገልግሎቶችንና የቴክኖሎጂ መፍትሔዎችን በመስጠት የተጀመረው የቢል ጌትስ ቢዝነስ፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣው፤ ቀን ከሌት በየእለቱ ለ16 ሰዓታት ያህል ተግቶ ስለጣረ ነው፡፡
በሰፈርና በከተማ ታጥሮ አልቀረም፡፡ በአገር ደረጃ ብቻ ሳይሆን በአለም ዙሪያ፤ የሰው ልጆችን ሕይወት የሚያሻሽሉ ቴክኖሎጂዎችን በመፍጠር የአለማችን ቁንጮ ሃብታም ለመሆን በቅቷል። በስኬታማነቱና በጀግንነቱ የተነቃቁ እልፍ ወጣቶችም፤ በየራሳቸው መስክ ተዓምር የሚያሰኝ የሃብት መጠን እንዲፈጥሩ አርአያ ሆኗቸዋል- በአሜሪካ ብቻ አይደለም፡፡ በቻይናም ጭምር እንጂ፡፡ ሃብትን እንደ ኩነኔ፣ በሚቆጥር ጥንታዊ ባህልና ባለሀብትነትን እንደ ወንጀል በሚቆጥር የሶሻሊዝም አስተሳሰብ ለድህነትና ለረሃብ ተዳርጋ የነበረችው ቻይና፤ “ባለሀብትነት ቅዱስነት ነው” በሚል ሃሳብ ነው የብልጽግና ጉዞ የጀመረችው፡፡ በእርግጥም ባለፉት 20 ዓመታት የቻይና ወጣቶች በአድናቆት ከሚጠቅሷቸው ጀግኖች መካከል፣ ቢል ጌትስ ተጠቃሽ መሆኑ አይገርምም፡፡ እኛም ብልጽግናን ከምር የምናከብር ከሆነ የቢዝነስ ስኬታማነቱ ትልቅ ቁምነገር መሆኑን በመገንዘብ፣ አክብሮትና አድናቆታችንን ለመግለጽ፣ የክብር ዶክትሬት ብንሰጠው መልካም ነበር፡፡ በእርግጥ ቢል ጌትስ ለኢትዮጵያ ብዙ የገንዘብ እርዳታ ሰጥቷል፡፡ ማመስገን ይገባል፡፡
ነገር ግን እርዳታና ምጽዋት፤ ለጊዜው ድህነትን ለመቋቋም ይጠቅም እንደሆነ እንጂ ለብልጽግና አያበቃም፡፡ የላቀ ክብር እና አድናቆት መስጠት ያለብን ለቢዝነስ ስኬታማነትና ለሃብት ፈጣሪነት ነው - ብልጽግናን የምናከብር ከሆነ፡፡ አሳዛኙ ነገር፤ ከእርዳታና ከተመጽዋችነት በተቃራኒ፣ የቢዝነስ ስኬትና ሃብት ፈጠራ ዋና የአገሪቱ የብልጽግና ተስፋዎች ናቸው የሚል መንግስት፤ ለቢል ጌትስ የክብር ዶክትሬት የምንሰጠው በሃብት ፈጣሪነቱና በቢዝነስ ስኬታማነቱ ሳይሆን በእርዳታ ለጋሽነቱ ነው ማለቱ ነው፡፡ ቢያንስ ቢያንስ፤ “ባለ ሃብትነቱንና ስኬታማነቱን እናከብራለን፤ እናደንቃለን፡፡ የዛሬው ሽልማት ግን ለሰጠን እርዳታ ምስጋናችንን የምንገልጽበት ነው” ብሎ መናገር ይቻል ነበር፡፡ ይሄም ይቅር፡፡ ግን፤ እርዳታ ለመስጠት የቻለው‘ኮ፤ በቢዝነስ ስኬታማነቱ ሃብት የፈጠረ ጀግና ስለሆነ ነው፡፡ ሃብት መፍጠር እንጂ ሃብት መስጠትማ ቀላል ነው፡፡ አርአያ አያስፈልገውም፡፡  

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
“ወራሪም ፈጣሪን ላያቅ
የጣለውን በስሏል እንጂ፣ ወድቋል ብሎ ግፉ ላያልቅ…”
ይላል ሎሬት ጸጋዬ፡፡ እኛም ዘንድሮ የጣልነውን “ወድቋል” ሳይሆን “በስሏል” የምንልበት ዘመን ይመስላል፡፡ በየዓለም ጥጉ ሁሉ የምታዩት ነገር “ወድቋል” ማለት ቀርቶ “በስሏል” ማለቱ የሰውን ልጅ የሚያግባባ ብቸኛው ቃል የሆነ ይመስላል፡፡
የምር ግን…ዓለማችን ችግሯ በዛሳ! አንዱ የቸገረው ምን አለ መሰላችሁ…“ምናልባት ይቺ ምድራችን የሌላ ዓለም ገሀነም ልትሆን ትችላለች፡፡”አሪፍ አባባል አይደል! አሁን፣ አሁን የምንሰማውና የምናየው ነገር ሁሉ…አለ አይደል…“የሰው ልጅ ወደ ድንጋይ ተመለሰ እንዴ!” ያስብላል፡፡
የምር እኮ… እንዴት ነው እውቀት እየበዛ ሄደ በሚባልበት ዘመን ይሄን ሁሉ ጭካኔ የምናየው! እናላችሁ…ምድራችን በአንዱ ሲብስባት በሌላው እንኳን እንዳንጽናና ‘የተካበ’ የሚመስለው ሁሉ እየተሰነጣጠቀ ግራ ገብቶናል። ሸሽተን የምንሸሸግባቸው የውጪ ‘ቻነሎች’ የሚያሳዩን ነገሮች ሁሉ “ይሄ ስምንተኛው ሺህ ሚሌኒየሙን አልፎ… አዘናግቶ መጣብን እንዴ!” ያሰኛሉ። (በነገራችን ላይ…አሁን ያለንበትን ዘመን ከኃይማኖታዊ አስተምህሮቶችና ትንቢቶች ጋር እያጣቀሱ ‘ጊዜው መድረሱን’ የሚናገሩ እየበዙ ነው።)
ቦምብ ከሚንዳት ምድር አላቆ አበባ የሚያብባት ምድር ያድርግልንማ! እናማ…የባሩድ ሽታ በጽጌረዳ መአዛ የተተካባት ምድር ያድርግልንማ!
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ይቺን ካወራናት እንድገማትማ…ሰውየው የገጠር ሰው ነው፡፡ እናላችሁ…የሰው ነፍስ ያጠፋና ፍርድ ቤት ይቀርባል፡፡ ታዲያ ‘ለማተቡ፣ ለክሩ’ የሚቆም ስለሆነ መግደሉን እንደሚያምን ለዘመዶቹ ይነግራቸዋል፡፡ ስለ ህጉ ብዙም ዝርዝር ስለማያውቅ የሚወሰንበትን ግን አላሰበውም። ታዲያማ፣ ችሎት ቀርቦ የእምነት ክሀደት ቃል ሊጠየቅ ሲል አጎቱ ማስጠንቀቂያ ሹክ ሊለው ጠጋ ይለዋል፡፡ ይሄን ጊዜ ዳኛው ያዩትና “እዛ’ጋ፣ ተጠርጣሪውን ምንም ነገር ማናገር ክልክል ነው!” ብለው ይቆጣሉ፡፡ ይሄኔ አጎትየው ወደኋላ ያፈገፍግና ምን ቢል ጥሩ ነው…
“ጌታዬ፣ ቢያምን እንደሚሞት፣ ቢክድ እንደሚተርፍ እሱ መች አጥቶት ነው እኔ የምነግረው!” ብሎ አረፈው፡፡
ዘንድሮ ያልሆነው ሆነ፣ የሆነው አልሆነም እየተባልን በአጠቃላይ “…እኛ መች አጥተነው ነው የሚነግሩን…” የሚያስብሉ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ በዓይናችን በብረቱ አጥርተን የምናየው፣ በጆሯችን አጥርተን የምንሰማው ነገር ተመልሶ ሲነገረን፡፡
እናላችሁ…አንዳንዴ ስለተለያዩ ነገሮች ሲወራ እኛ ያለንባት ራሷ ጦቢያ መሆኑን ረስተን… “እስቲ ይቺን የምታወሩላትን አገር አሳዩን… ልንል ምንም አይቀረን፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ስለ መግባባት ካወራን ይቺን ስሙኝማ… ሰውየው ክፍል ውስጥ አማርኛ እያስተማረ ነው፡፡ ደግሞላችሁ…ተማሪዎቹ ገና ጀማሪዎች በመሆናቸው ስለ ስዋስው ምናምን ብዙም የሚያውቁት ነገር አልነበረም፡፡
እናላችሁ…በሚገባ ሳያስረዳቸው ምን ብሎ ይጠይቃቸዋል፣ “‘አበበ ከበደን በዱላ መታው’ የሚለው አረፍተ ነገር ውስጥ ግሱ የምን ግስ ነው?” ብሎ ይጠይቃል፡፡
አንደኛው ተማሪ ምን ብሎ መለሰ መሰላችሁ…“የወንጀል ክስ ነው፡፡” ልክ ነዋ…በዱላ መምታት ወንጀል ነዋ! “በዱላ መታው” ካሉ በኋላ ወላ ‘ገቢር ግስ’፣ ወላ ‘ተገብሮ ግስ’ ብሎ ነገር የለማ! ቂ…ቂ…ቂ… (አስተማሪው ያቀረበው የምሳሌ ዓረፍተ ነገር “አበበ ከበደችን በከንፈሮቹ ሳማት…” ቢሆን ኖሮ ግሱ ‘ተሻጋሪ’ ግስ ይሆን ነበር! ሳይገባኝስ!)
እናማ…ችግሩ የመላሹ ሳይሆን የአስተማሪው ነው፡፡ ዘንድሮም አብዛኛው ችግር የእኛ ‘የመረጃ’ ተቀባዮች ሳይሆን የእነሱ ‘የመረጃ’ ሰጪዎቹ ነው። የእውነት መረጃ የሚሰጡን ሳይሆን እኛ ጥቁር ያልነውን እነሱ “ቀይ ነው ብያለሁ ቀይ ነው…” አይነት ነገር ይሆናል፡፡ ይሄኔ ታዲያ እኛ ደግሞ…ጮክ ብለን ባንናገር እንኳን በሆዳችን “…እኛ መች አጥተነው ነው የሚነግሩን…” እንላለን፡፡
(ያን ሰሞን የድራፍት ዙሪያ ‘ሀሜታ’ ላይ “እንኳን ጮክ ብለን ጠንከር አድርገን ስንተነፍስም ዓይን በዝቶብናል…” ያልከው ወዳጄ ‘አድናቂህ’ ነኝ።) በነገራችን ላይ…እግረ መንገዴን የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ…በአንድ ተጠባባቂ ተጫዋች ብቻ የነጥብ ዓለም አቀፍ ጨዋታ በመጫወት ከዓለም ስንተኛ ነን! አይ ጦቢያ! እኔ የምለው… ‘እሱ ሰፈር’ በዛ ሰሞን “ተሽሎታል…” ምናምን ሲባል አልነበረም እንዴ! ኮሚክ ነገር እኮ ነው…ፓስፖርት ላይ የተጻፈ ዓመተ ምህረት አይቶ ‘ለመደመርም’ ካሽ ሬጂስተር ማሺን ምናምን ሊያስፈልገን ነው ማለት ነው!
ደግሞላችሁ የኳስ ነገር ካነሳን አይቀር… ኳስ ጨዋታዎች በቲቪ ላይቭ ሲተላለፍ ‘ኮሜንተሪ’ የሚያሰሙት…ሁሉም እንቅስቃሴ ‘ሙሉ አረፍተ ነገር’ መሆን አለበት እንዴ! “የእንትን በረኛ ለመሀል ተከላካዩ…” እንዳቀበለው በመግለጽ የተጀመረው ዓረፍተ ነገር እስኪጠናቀቅ ኳሷ በሰባት በስምንት እግሮች ተነክታ ትመለሳለች። እንዴ… ጨዋታውን እኛም እያየነው እንደሆነ ልብ ይባልልና! አለበለዛ “ስምንት ቁጥሩ አንጋጋው አናጌ ከባላጋራ ተጫዋቾች መሀል ከፍ ብሎ ዘሎ ኳሷን በጭንቅላቱ ገጫት…” አይነት ነገር ግስ፣ ስም፣ ተውላጠ ስም፣ ተሳቢ፣ ቦዝ አንቀጽ ምናምን አሥራ ስምንት የንግግር ክፍል ያለበት ይመስላል፡፡ ዓረፍተ ነገሩ ሲጀመር ምጥ የጀመራት ሲያልቅ ልትወልድ ትችላለች እኮ! (ቂ…ቂ…ቂ… እኛም የማጋነን ዕድል ይድረሰና!)
የምር ግን ላይቭ ኮሜንታሮቻችን ዘዴያቸውን መፈተሽ ያለባቸው ይመስለኛል፡፡  ደግሞ የተጫዋቹ ቁጥር እየቀረ ስም ከእነ አባቱ ሳይቀር ሁሉም መባል የለበትም፡፡ አንጋጋው አናጌ በአንድ ጨዋታ ላይ ሙሉ ስሙ የተጠቀሰውን ብዛት ከቄስ ትምህርት ቤተ ጀምሮ መዝገቦች ላይ የተጻፈው ተደምሮ አይደርስበትም፡፡ (‘ማጋነን’ ለመደብኝ ማለት ነው!)
ከተጨዋወትን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…‘በኮሚዋ’ ሩስያ ዘመን የኮሚኒስት ፓርቲው የምስረታ በዓል እየተከበረ ነበር፡፡ እናላችሁ…በአንድ የሀገሪቱ አውራጃ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ልዩ ዝግጅት ነበር፡፡ በዝግጅቱም ላይ የአካባቢው የፓርቲ ሊቀመንበር ንግግር ያደርጋል።
“የተወደዳችሁ ጓዶች!” ከአብዮቱ በኋላ ፓርቲያችን ያስመዘገባቸውን ስኬቶች ልብ በሉ። ለምሳሌ እዚህ አጠገቤ ያለችውን ማሪያን ተመልከቱ፡ ከአብዮቱ በፊት ምን ነበረች? ማንበብ መጻፍ የማትችል መሀይም አርሶ አደር፡፡ የነበራት አንዲት ቀሚስ ብቻ ነበረች፣ ጫማም ስላልነበራት በባዶ እግሯ ነበር የምትሄደው፡፡ አሁንስ? አሁን በአካባቢያችን ቤት ለቤት በመዞር ወተት በመሸጥ ትታወቃለች፡፡ ወይንም ኢቫን አንድሪቭን ተመልከቱት፡፡
በሰፈራችን የነጣ ድሀ ነበር፡፡ ፈረስ የለው፣ ላም የለው፣ መጥረቢያ እንኳን የለውም ነበር። አሁንስ? አሁን ትራክተር አሽከርካሪ ነው። ደግሞም ሁለት ጫማ አለው፡፡ ዕድሜ ለአብዮቱ ሁለት ጫማ! ወይ ደግሞ ትሮፊም ሴሜኖቪች አሌክሲቭን ተመልከቱት፡፡ የለየለት ወሮበላ፣ ሰካራምና መቼም የማይጸዳ ነበር፡፡ ያገኘውን ምንም ነገር ከመስረቅ ስለማይመለስ ማንም ሰው አያምነውም ነበር። አሁን ግን ዕድሜ ለአብዮቱ የፓርቲ ኮሚቴው ጸሀፊ ሆኗል።”
እኔ የምለው…እኛ ዘንድ ተመሳሳይ ‘ስኬቶች’ ካሉ ይገለጹልንማ!
እናላችሁ… በዚህ የቴክኖሎጂ ዘመን፣ በእነፌስቡክ ዘመን፣ በትዊተር ዘመን፣ በዩ ቲዩብ ምናምን ዘመን “…እኛ መች አጥተነው ነው የሚነግሩን…” ባንባባል አሪፍ ነው፡፡ አሥር ወር ገበያ ላይ ቆይቶ መውጣቱን እንኳን ሰው ነገሬ ያላላውን አልበም “በከፍተኛ ደረጃ እየተሸጠ ነው…” አይነት ነገር ስንባል፤…ሰው ሳይበዛ ገብተን እንደ ቲያትር ቤት መዳፋችን የዝንጀሮ እንትን እስኪመስል ድረስ ካላጨበጨብን አስተናጋጆች ብቅ የማይሉበትን ሬስቱራንት “በዚህ ሬስቱራንት ደንበኛ ንጉሥ ነው…” ምናምን ስንባል፤ ሀሳብ የሚሰጥ ጠፍቶ ሰብሳቢዎቹ… አለ አይደል… የስብሰባው መሪዎችም፣ የስብሰባው ንቁ ተሳታፊዎችም እነሱ ብቻ በሆኑበት “ከፍተኛ የሀሳብ ልውውጥ የተደረገበት ስብሰባ…” ሲሉን…በቃ ቀሺም ነገር ነው፡፡
በትንሹም በትልቁም “…እኛ መች አጥተነው ነው የሚነግገሩን…” የማንባባልበትን ዘመን ያምጣልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Published in ባህል

ባለፈው ሳምንት አዲስ አድማስ ጋዜጣ “ጦማሪያኑና ጋዜጠኞቹ በሽብርተኝነት ተከሰሱ፤ ተከሳሾቹ ከግንቦት ሰባትና ከኦነግ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ተገለፀ”  በሚል ርዕስ በፊት ለፊት ገጹ ያወጣውን ዘገባ ሳነብ የተሰማኝ ድንጋጤና ሃዘን ይህ ነው የማይባል ነው፡፡ አዕምሮዬ ደጋግሞ ከጦማሪያኑ መካከል አንዷ የሆነችውንና በአሁኑ ሰዓት በእስር ላይ የምትገኘዋን ማህሌት ፋንታሁንን (ማፊ) አስታወሰ፡፡
ወጣት ናት፡፡ እኔ እስከማውቃት ድረስ ይህ ነው የማይባል የአገር ፍቅር ያላት! መሻሻል፣ መለወጥ፣ ማደግ የምትሻ ቀልደኛ! ማንበብና መወያየት አጥብቃ የምትወድ …. በቃ እኔ የማውቃት ማፊ እቺ ናት፡፡  
እኔ፣ ማፊና ሌሎች ወጣቶች
ጊዜው 1999 ዓ.ም ላይ መሆኑ ነው፡፡ የዓለም ባንክና ብሪትሽ ካውንስል፣የወጣቶችን የአመራር ብቃት ለማዳበርና ለማብቃት የሚያግዝ አንድ ስልጠና ለመስጠት ማስታወቂያ ያወጣሉ። የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የሚታገዙ የወጣት ድርጅቶች አመራሮች፣ ጋዜጠኞች፣ በግል የቢዝነስ ስራ የተሰማሩና ሌሎችም ስልጠናውን ለመሳተፍ አመለከትን፡፡ ለስልጠናው የሚፈለገው የተወሰነ ወጣት ስለነበር፣ የመለያ መመዘኛዎች ወጥተውልን በግምት 25 የምንሆን ወጣቶች ስልጠናውን የመካፈል ዕድል አገኘን፡፡ ከእነዚያ ተሳታፊዎች መካከል ማህሌት ፋንታሁን (ማፊ) አንዷ ነበረች፡፡ በዚህ አጋጣሚ ነው እኔና ማፊ የተዋወቅነው፡፡
“Debate to Action!”
የዓለም ባንክና ብሪቲሽ ካውንስል እኛን ለማሰልጠን የተጠቀሙበት መሪ ቃል “Debate to Action!” የሚል ሲሆን ስልጠናው፣ ውይይትና ክርክር አንድን ነገር ተግባራዊ ለማድረግ ምን ያህል ጠቀሜታ እንዳለው የሚያስገነዝብ ነበር፡፡ እውነትም በወቅቱ በበርካታ አገራዊ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ በቡድን  እየተከፋፈልን ውይይትና ክርክሮችን አደረግን፡፡
በዚያ ስልጠና ከማፊ ሌላ ሊሳተፉ መጥተው ከተዋወቅኋቸውና በኋለኛው ዘመኔም ወዳጅ ካደረግኋቸው ወጣቶች መካከል ከወር በፊት “ፍርድ ቤት ግቢ ውስጥ ፎቶ ስታነሳ ታይተሃል” ተብሎ ለአጭር ቀን ታስሮ የተለቀቀው የህግ ባለሙያው ኪያ ፀጋዬ፣ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የሚሰራው ዶ/ር ኤፍሬም ተክሌ፣ በአፍሪካና በተለይም በምስራቅ አፍሪካ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ትንታኔ በመስጠት የሚታወቀውና በወቅቱ “አፍሮ ፍላግ” የተሰኘውን የወጣቶች መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት በመምራት ላይ የነበረው ኢዮብ ባልቻ፣ በፈረንሳይ ፓሪስ በአካባቢ ጥበቃ “ሞዴል ወጣት” ተብሎ የተሸለመውና በአሁኑ ሰዓት በዓለም የሙቀት መጠን መጨመር ዙሪያ እየሰራ የሚገኘው አለማየሁ አካሉ (ሶረኔ)፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማስተርሷንና ከቤልጂየም ዩኒቨርሲቲ ተጨማሪ ዲግሪዋን ያገኘቺው ሶፊያ ዓሊ፣ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቶ ከማንችስተር ዩኒቨርሲቲ ማስተርሱን ያገኘውና በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ የሰላምና ልማት ዓለም አቀፍ ተቋም ባልደረባ የሆነው  ይነበብ ንጋቱ ---- ይገኙበታል፡፡
ከዚያ ስልጠና በኋላ አብዛኞቻችን ስለአገራችን በተለየ መልኩ ማሰብ ጀመርን፡፡ የእኛ ተሳትፎ እስካልታከለበት ድረስ አገር ወደ የትም ማደግ እንደማትችል ገባን፡፡ የዘር፣ የቀለም፣ የጎሳ ወዘተ ልዩነት ሳናደርግ በአገር ጉዳይ ሁላችንም ተገቢውን ውይይትና ክርክር በማድረግ፣ ለአገር ይበጃል ያልነውን ለመንግስታችንና ለሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ለማድረስ የየበኩላችንን ጥረት ማድረግ ቀጠልን፡፡
በጋዜጦች፣ በመፅሄቶች፣ በተለያዩ ስልጠናዎች፣ በትምህርት ቤቶችና ከትምህርት ቤቶች ውጪ በተመሰረቱ የወጣት ክበባት፣ ማህበራትና ድርጅቶች፣ በዩኒቨርሲቲዎች፣ በሙያ ማህበራትና በመሳሰሉት ውስጥ ንቁ ተሳታፊዎች በመሆን “እኛም ስለአገራችን ያገባናል! “ አልን። ከስልጠናው ተሳታፊዎች ውስጥ እንደነ ስዩም ቲቶና ተክለሚካኤል (ቲ.ማይክ) የመሳሰሉ ሃቀኛ  የኢህአዴግ ደጋፊዎች ቢኖሩም ሁላችንም በዕውነተኛ ወዳጅነት ውይይታችንን በነፃነት ስናካሂድ ቆይተናል፡፡  
ማንም ማንንም አይፈርጅም፤ ማንም የማንንም ሃሳብ እንጂ ማንነት አያጣጥልም፡፡ ማንም በማንም ተፅዕኖ ስር አይወድቅም፡፡ ሁላችንም ከዚያ ስልጠና በተማርነው ፅኑ ስነ-ስርዓት መሰረት፣ ለክርክርና ለውይይት ደንብና ስርዓት ተገዢዎች ነበርን፡፡
እኔ በወቅቱ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ድርጅት፣ የህፃናትና የወጣቶች ፕሮግራም አዘጋጅ ስለነበርኩ ከሁሉም ተሳታፊዎች ጋር በቀላሉ ለመግባባት አልቸገረኝም፡፡ ታዲያ በእኔ ግምት በዕድሜም ሆነ በትምህርት ደረጃ እንደዚሁም በልምድም ቢሆን ከሁላችንም የምታንሰው ማህሌት ፋንታሁን (ማፊ) ነበረች፡፡
የስልጠናችን ትኩረት
“Debate to Action!” በይበልጥ ያተኮረው በዓለምና በተለይም በአፍሪካ አገራት የዕድገት ሞዴሎች፣ በምዕተ-ዓመቱ የልማት ግቦች፣ በአመራር ጥበብና በአጠቃላይ በልማት ዙሪያ የወጣቶች ሚና ምን መሆን አለበት በሚሉት ጉዳዮች ላይ ነበር። የድህነታችን መንስኤዎች፣ በድህነታችን ሳቢያ እየኖርነው ስላለው አሳፋሪ የኑሮ ደረጃ፣ ድህነትን ስለሚቀንሱልን የልማት ሞዴሎች፣ ስለአደጉ አገራት ተመክሮ፣ ስለ አስተሳሰባችን፣ ስለጊዜ አጠቃቀማችን ወዘተ---የስልጠናችን ዋና ዋና ትኩረቶች ነበሩ። ስልጠናውን ከሰጡን ባለሙያዎች መካከል፣ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት የመንግስት ቃል አቀባይ፣ በኋላም የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ዋና ስራ አስኪያጅ የነበሩት ወ/ሮ ሠሎሜ ታደሰ እንደነበሩ አስታውሳለሁ፡፡
ከብዙ ጊዜ በኋላ ማፊን አግኝቼ ሳወራት፣ በፖለቲካም ሆነ በአጠቃላይ በልማት /ዴቨሎፕመንት/ ዙሪያ ያላት አስተሳሰብ በእጅጉ አደገብኝ፡፡ ስልጠናው መነሻ ሆኗት ከዚያ በኋላ በርካታ መፃህፍትን እንዳነበበች፣ ከባለሙያዎች ጋር እንደምትወያይ፣ በተለያዩ አዕምሮን የሚገነቡ ስልጠናዎች ላይ በተደጋጋሚ እንደምትሳተፍ ገመትኩ፡፡ ሆኖም ግን በእነዚያ ቅልጥ ያሉ የፖለቲካና የአገር ወሬ ውስጥ ገብተን ውይይት ባደረግንባቸው ወቅቶች አንድም ቀን ፅንፍ ይዛ፣ ልክ አልፋ ስትከራከርና ስታወራ ሰምቻት አላውቅም፡፡
የፌስ ቡክዋ ማፊ
በእርግጥ እንደማናችንም አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ፣ ማፊም ያየቻቸውንና ስህተት ነው ብላ የምታስባቸውን ፖለቲካዊ ትዝብቶች ፌስቡክ ላይ በመለጠፍና በማካፈል ትታወቃለች፡፡ ሆኖም ግን እኔ እስከማውቀው ድረስ አንድም ፅሁፏም ሆነ የለጠፈቻቸው ስዕሎች ፅንፈኝነትን ሲያሳዩ፣ አክራሪነትን ሲያበረታቱ፣ ሽብርተኝነትን ሲሰብኩ አላስተዋልኩም፡፡ ይልቁኑም በመንግስትም ሆነ በተቃዋሚዎች ዘንድ ስለሚታዩ ክፍተቶች በመጠቆም፣ ለአገር ጠቃሚ የሆነ አስተዋፅኦ ማድረጓን ብቻ ነው የማስታውሰው፡፡
ግጥም ወዳጅዋ ማፊ
“ግጥምን በጃዝ” በሚል ቀደም ብሎ በዋቢሸበሌ፣ ከዚያም በራስ ሆቴል ውስጥ በሚካሄደው ፕሮግራም ላይ ማፊን የፈለጋት አያጣትም፡፡ ግጥም ታደንቃለች፡፡ ነፍሷን ለነካላት ግጥም ከመቀመጫዋ ተነስታ በፉጨት በማደበላለቅ ሞራል ትሰጣለች። እንዳስተዋልኳት የእርሷ የነፍስ ግጥሞች በአገር ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ናቸው፡፡ ስሜታቸው በልዩ ሁኔታ ይገቡዋታል፡፡ ማፊ ግን ስትገጥምም ሆነ ግጥምን ለሽብር ዓላማ ስታውል አይቼም ሰምቼም አላውቅም፡፡
ሰራተኛዋና ግድ የለሽዋ ማፊ
ትዝ እንደሚለኝ ከሆነ ማፊ ስራ የጀመረችው የርቀት ትምህርት በሚሰጥ ተቋም ውስጥ ሲሆን እስከታሰረችበት ጊዜ  ድረስ በጤና ጥበቃ ሚ/ር ውስጥ ትሰራ እንደነበር ነው የማውቀው፡፡ ማፊ ፀጉሩዋን እንደ ሴት በወጉ ለመሰራት፣ በአልባሳትና በኮስሞቲክስ ለመዘነጥ ምንም ግድ የሌላት እንደሆነች ታዝቤአለሁ፡፡ ሁልጊዜ ሳገኛት ጅንስ ሱሪና ቲ-ሸርት አድርጋ ከኋላዋ ቦርሳ ታዝላለች፡፡
የኢትዮጵያና ናይጄሪያ ጨዋታ ዋዜማ
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከናይጄሪያ ጋር ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ ወሳኝ ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚያደርግበት ወቅት ላይ ነው። በዋዜማው ማታ ካዛንችስ በሚገኘው “በዕምነት ሬስቶራንት” ከማፊ ጋር ያሳለፍነው ጊዜ አይረሳኝም። አብዛኞቻችን በዚያ ስልጠና ላይ ተሳታፊ የነበርን ጓደኛሞች፣ የኢትዮጵያን ባንዲራ ለብሰን ከማፊ ጋር የመጨረሻውን እራት ተቋድሰናል፡፡ ያን ቀን ስለአገራችን በርካታ ጉዳዮችን አንስተን ያወራን ቢሆንም ማናችንም ፅንፍ ይዘን አልተከራከርንም፤ ከማናችንም ሽብርና ሽብርተኝነት የሚል ፅንሰ-ሃሳብ ሲንፀባረቅ አልተሰማም፤ ማናችንም ማንንም በጠላትነት አልፈረጅንም፡፡
በዚያ አስደሳችና የማይረሳ ምሽት ማፊ አንድ ነገር አስታወሰች፡፡ ስለ ስልጠናችን፡፡ ለእርሷ የፖለቲካ ህይወት መጀመሪያ፣ ያ…የዓለም ባንክና የብሪቲሽ ካውንስል ስልጠና መሆኑን ተናገረች። ቀደም ብሎ  ምንም የልማትም ሆነ የፖለቲካ ግንዛቤ እንዳልነበራት መሰከረች፡፡ ከዚያ በኋላ ግን የሰማሁት መታሰሯንና የማታ ማታም በሽብርተኝነት ክስ እንደተመሰረተባት ነው፡፡
የሽብር ትርጉሙ ግራ አጋባኝ
ማፊ እስር ቤት ገባች ተብሎ የተነገረኝ ቀን፣ የሽብርና የሽብርተኛ ትርጉሙ ከዕለት ወደ ዕለት እየቀለለና ወደ እያንዳንዳችን ደጃፍ እየመጣ እንደሆነ ተሰማኝ፡፡ በተለይም ደግሞ ጋዜጠኞችና ጦማሪያኑ በሽብርተኝነት ክስ እንደተመሰረተባቸው ስሰማ የሽብር ትርጉሙ ግራ አጋብቶኛል፡፡ ማፊ ሽብርተኛ ከሆነች ሽብር ቀላልና ብዙም የሚያስፈራ ነገር አይደለም ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም በማፊ ዕድሜና ተመክሮ የሚቀነባበር ሽብር የትም የሚያደርስ አይመስለኝም፡፡
እኔ እስከማውቀው ድረስ ማፊ ጮክ ብላ ስለ ኢትዮጵያ ከመዘመር ውጪ አንድም ቀን የሽብርተኝነት ባህሪም ሆነ አስተሳሰብ ስታራምድ አልገጠመኝም፡፡ አራምዳለች ከተባለም የፍርድ ውሳኔውን ስሰማ ምን እንደሚሰማኝ አላውቅም፡፡
የማፊ ታናናሾችና ፖለቲካ
እንኳን የወጣት ሴቶችና የወጣት ወንዶችም ፖለቲካዊ ተሳትፎ እየቀጨጨና እየሞተ ባለበት በዚህ ወቅት (ፖለቲካ በራሱ ከሴቶች ለወንዶች የሚቀርብ ስለሚመስለኝ) እንደ ማፊ ዓይነቶቹ ልዩ የአገር ፍቅር ያላቸው፣ ፖለቲካን ለማወቅና ለመማር ብሎም በንቃት ለመሳተፍ የሚፈልጉ ወጣቶች መታሰር ጉዳቱ ከባድ ነው፡፡ የማፊ ታናናሾች ተመክሮዋን በመውሰድ የፖለቲካን መዝሙር በርቀት ብቻ መዘመራቸውን ይቀጥላሉ፡፡ እሱም ከደፈሩ ነው፡፡ ይህ ታላቅ የአገር ኪሳራ ነው፡፡ አገር መልሳ ልትከፍለው የማትችለው ታላቅ ኪሳራ! ከመስመር የወጣ አካሄድ አላት ተብሎ ቢታመን እንኳን መንግስት ሆደ ሰፊ ሆኖ በምክር ብቻ ሊመልሳት ይገባ ነበር የሚል እምነት አለኝ፡፡ እቺን አንድ ፍሬ ወጣት “ሽብርተኛ” ብሎ መሰየሙ ትንሽ ነፍሳት ላይ  መድፍ እንደመተኮስ ነው፡፡ ይህ ደግሞ መንግስትን  ትዝብት ላይ ይጥለዋል፡፡
እኔ በብዙ አጋጣሚዎች ስለማውቃት ማፊ እንዲህ ፃፍኩ እንጂ ስለተቀሩትም ታሳሪዎች የሚያውቋቸው ሰዎች ብዙ ሊሉ ይችላሉ፡፡ ወጣቶች በተለይም ደግሞ ወጣት ሴቶች እንዲህ ከጅምራቸው በእስርና እንግልት ተደናግጠው ከፖለቲካው መድረክ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከመሰወራቸው በፊት የአገር ሽማግሌዎች፣ ልባም የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ ራዕይ ያላቸው የመንግስት ባለስልጣናት (ካሉ) እና መላው ዓለም ሊረባረቡላቸው ይገባል፡፡
ባለ ድብቅ ልቧ ማፊ?
ምናልባት መንግስት እንደሚለው፤ማፊ ከእኛ ከወዳጆቿ ተደብቃ ልቧን ለሽብርተኞች ቡድን ሰጥታ ይሆን?   ይህ ለእኔ ዝሆን በመርፌ ቀዳዳ አለፈች የማለት ያህል ቢሆንም መንግስት ግን “መረጃ አለኝ፤ ደርሼብሻለሁ” ብሏታል፡፡ እናም ባሳለፍናቸው በእነዚያ ተወዳጅና ተናፋቂ ጊዜያት ስም፣ ማፊን ከእንዲህ ዓይነቱ ክስ እንዲሰውራት ወደ ፈጣሪዬ ተማፅኖዬን  አቀርባለሁ፡፡

አንድ የአፍጋኒስታኖች ተረት እንዲህ ይላል፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ሰው ሚስቱ ድርስ-እርጉዝ ሆና ስለነበር ለሚወለደው ወይም ለምትወለደው ልጅ አልጋ ሊያሰራ፤ ወደ አልጋ ሰሪ ሄደ፡፡  ያ አልጋ ሰሪ አናጢ፤
“ምን ፈልገህ ወደኔ መጣህ?” ሲል ይጠይቃል፡፡
“ለልጄ አልጋ ላሰራ ፈልጌ ነው” ይላል አባት፡፡
“መልካም፡፡የህፃን ልጅ አልጋ ግምቱ የታወቀ ስለሆነ አሳምሬ እሰራልሃለሁ” አለው፡፡
አባት፤ በጉዳዩ ተስማምቶ፤
“በል እንካ ቃብድህን፡፡ አደራ ደህና አድርገህ ስራልኝ” ብሎ ገንዘቡን ሰጠው፡፡
አባት የልጁ መወለድ እየቀረበ ስለመጣ ወደ አናጢው እየሄደ፤
“እህስ፤ ምን አደረስክልኝ?” ይለዋል፡፡
“ቆይ ትንሽ ጠብቅ” ይላል አናጢ፡፡
አባት ሌላም ቀን ይመጣል፡፡
የአናጢው መልስ፤
“ቆይ ትንሽ ጠብቀኝ” ሆነ፡፡
በዚህ ማህል ልጁ ተወለደ፡፡ አደገ፡፡
ጎረመሰ፡፡ ጎለመሰና ሚስት አገባ፡፡ ሚስቱ ፀነሰች፡፡ አረገዘች፡፡
ልጁ እንግዲህ አባት ነውና፤ ኃላፊነት አለበትና፤ ወደ አባቱ ሄዶ፤
“አባቴ ሆይ! መቼም አንተ ልምድ አለህና ለሚወለደው ልጄ አልጋ ከየት እንደምገዛለት ንገረኝ?” አለው፡፡
አባትየውም፤
“የውልህ ልጄ! የዛሬ ሃያ ዓመት፤ ለአንድ አናጢ አንተ ስትወለድ የምትተኛበት አልጋ ላሰራ ቀብድ ሰጥቼው ነበር፡፡ ሂድና አልጋው አልቆ ከሆነ፤ ቀሪውን ከፍለህ አልጋውን አምጣና ልጅህ ይተኛበታል!” አለው፡፡
ልጅየውም ተደስቶ ወደ አናጢው ሄደና፤
“ጌታው፤ ከዚህ ቀደም አባቴ አልጋ ሊያሰራ ገንዘብ ከፍሎህ ነበር፡፡ እሱን ለመውሰድ ነበር የመጣሁት”
አናጢውም፤
“እናንተ ሰዎች አልጋ በጥድፊያ አይሰራም፡፡ አትጨቅጭቁኝ፡፡ አታጣድፉኝ፡፡ እኔ የጥድፍ ጥድፍ ስራ አልወድም፡፡ ካልፈለጋችሁ ገንዘባችሁን ልመልስላችሁ እችላለሁ!” አለ፡፡
                                               *            *              *
ለልጅ አልጋ ማሰራተን የመሰለ ቁምነገር የለም፡፡ ትውልድን እንደመታደግ ነው፡፡
ከሃያ ዓመት በኋላ “አታጣድፉኝ!” ከሚል ይሠውረን!
የአልጋ ነገር ሁሌም አሳሳቢ ነው፡፡ አዲስ ህፃንም ይተኛበት የቆየ፤ ችግር አያጣውም፡፡ አልጋ ሲሰራ ጥድፊያ አይወድም፡፡ ሃያ ዓመት ቢፈጅም ጥድፊያ አይወድም፡፡ ሰሪውም በቀላሉ አይለቅም! “የጥድፊያው ጥቅም ለሠሪው ነው ለአሠሪው?” ነው ጥያቄው፡፡ ማስተዋልን የመሰለ ነገር የለም ዞሮ ዞሮ፡፡
ምንም ሆነ ምን ድህነትን ማሸነፍ ግዳችን ነው! “ነጭ ደሀ ነጭ ብር ይወልዳል” ቢሉም አበሳውን ማስታወስ ተጨምሮ መሆን አለበት፡፡ ቢያንስ እንደ ፀሐፌ-ተውኔት “ስደተኛ ዘላን ሶማሌ በሄደበት ሣር ወይም አሣር ይጠብቀዋል” የሚል የአምሣ ባምሳ ግምት (Probability) ፈጥሮ ስለአገር ማሰብ ብልህነት ነው፡፡ ምሁሩም፣ መሀይሙም፣ ጠቢቡም፣ ግብዙም ስለአገር ጨለምተኛ (Pessimist) ሆኖ የትም አንደርስም!!
እንደሌላው ዓለም ሁሉ፤ ያለጥርጥር ልማት በኢትዮጵያ፤ ሂደት እንጂ ግብ ብቻ አይደለም፡፡
የጥንቱን የጠዋቱን የሀገራችንንና የውጪውን አገር ልማታዊ መንፈስ እንድናይ ይረዳን ዘንድ ጸጋዬ ገ/መድህን በምኒልክ አንደበት የሚከተለውን ይለናል፡-
“አውሮጳውያን የእጅ-ሥራ ዕድገታቸው፣ የዘመናዊ ሥልጣኔያቸው፣ የቱን ያህል ይደንቃል፡፡ እቴ ጣይቱ፡፡ መሣሪያ፣ መኪና፣ ፋብሪካ፣ የባህር መልህቅ፣ የመሬት መንኮራኩር ሥራቸው የቱን ያህል ይመጥቃል፡፡ የመንገድ ድልድያቸው፣ ወፍጮአቸው፣ ትምህርታቸው፣ እርሻቸው፣ ባንክ የሚሉት የገንዘብ ብልፅግና ዘዴአቸው፣ አውራ ጎዳኖቻቸው፣ ውሃ በቧንቧና ቃል በሽቦ እሚስብ፣ ነፋስ መላላኪያቸው፣ ብርሃን በክር እሚጠልፍ የሌት ሻማቸው፣ ሰፊ ከተማ ሙሉ ከፋሲል ግንብ የሚበልጡ ህንፃዎቻቸው፣ እቴ ጣይቱ አባ ማስያስና ኢንጂነር ኢልግ አጫውተውሽ የለ?! ብቻ ወደኛ የሚልኩብን ጦራቸውን ብቻ ነው፡፡”
ከላይ የተጠቀሰውን ስንመረምር፤
ዕደ ጥበብ ከዚያ ተነስቶ ዛሬ የት ደረሰ? ፋብሪካ የት ደረሰ? ባህርና ትራንዚት ምን ያህል ተራቀቀ? ትራንስፖርትና መገናኛ ምን ያህል አዘገመ ወይም ፈጥኖ ሄደ? የመንገድ፣ የድልድይ ሥራ ምን ያህል ረቀቀ? እርሻ ምን ያህል ሜካናይዝድ ሆነ? (በደርግ ዘመን ከፊል-ካፒታሊዝሙ ይስፋፋ መስሏቸው ትራክተሮች አስመጥተው “በሶሻሊዝም ተወረሰብኝ!” የሚሉ (ኮማንድ - ኢኮኖሚ ነብሱን ይማረውና) አንድ ባለሀብት፤ “ከጓድ ሊቀመንበር ጋር ወደፊት!” እና “ሶሻሊዝም ይለምልም” የሚል መፈክር ባዩ ቁጥር፤ እጃቸውን በጭብጨባ እያጣፉ “አጀብ!... ትራክተር!” ይሉ ነበር አሉ፡፡
የዛሬ ኢንቬስተር ይሄን አይልም ብለን ተስፋ እናደርጋለን! የባንክ ሥርዓታችንስ የት ደረሰ? ባንክ ውስጥ ካለን ገንዘብና በየሰዉ ትራስ ስር ካለው ገንዘብ የቱ ይበዛል? ሁለቱንም ነብሳቸውን ይማርና የቀድሞው መሪ ለባንኮች፤ “ከእናንተ አየለ (አይ.ኤም.ኤፍ) ይሻላል፡፡ ገንዘቡ በአጁ  አለ፡፡ ያንቀሳቅሰዋል!” ብለው ነበር አሉ፡፡ “ነፋስ መላላኪያችን” የት ደረሰ ማለት ያባት ነው (3G እና 4G እንዲሉ!) ብርሃን በክር የሚጠልፍልን መብራት ኃይልስ? ብሎ መጠየቅም ያባት ነው፡፡ ግንባታና ህንፃዎቻችንስ? ሰው ሰው ይሸታሉን? ለኢኮኖሚያዊ ዕድገታችን ያላቸው አስተዋፅኦ የሚተነትንልን የቱ ኢኮኖሚስት፣ የቱስ ባለሥልጣን ነው? ማንም ይሁን ምን፣ ገዢም ይሁን ተገዢ፣ ባለሃይማኖትም ሆነ ኢሃይማኖታዊ፣ የተማረም ሆነ ያልተማረ፣ አገር ውስጥ ያለም ሆነ ዲያስፖራ፣ ሀሳባዊም ሆነ ቁስ-አካላዊ፣ የእኛም ይሁን የውጪ ኃይል… ምኒልክ እንዳሉት… “ወደኛ የሚልኩት ጦራቸውን ብቻ” የሚለውን ነዋሪው ዜጋ እንደምን ያየዋል? መባባል አለብን፡፡ ሁሉ ነገር መጨረሻው ፀብ መሆኑን እንደምን እንየው? መቼ ነው ስለ አዎንታዊ ማንነታችን ደርዝ ያለው ግንዛቤ እምንጨብጠው?
እነዚህን ጥያቄዎች እያሰላሰልን ከገዢም ያልሆኑ ከተገዢም ያልሆኑ “የአየር ባየር ነጋዴዎች” እንዲሉ፤ “የአየር ባየር ፖለቲከኞች” ኋላ የአገር ውስጥ ገቢ መስሪያቤት (ፖለቲካ ሲገባው) የማይምራቸው እንደማለት፤ ፍፃሜያቸው መሬት የሆነ፤
“ጠላትማ ምን ጊዜም ጠላት ነው
አስቀድሞ መግደል አሾክሿኪውን ነው”  
እንደሚባሉ ያሉ አያሌ ናቸው፡፡ “መንገድ ሲበላሽ ትራፊክ ይበዛል፡፡ አገር ሲበላሽ ጃርት ያፈራል” የሚባለውን የጥንት አባባል ዛሬም ልንደግመው ተገደናል፡፡ ይህን ጉዳይ በትግሪኛ ተረት ብናስቀምጠው፤ “ጫማ ምን ክብር ቢኖረው፤ ሁል ጊዜም እግር ሥር ነው” ይሆናል!!  


Published in ርዕሰ አንቀፅ
Page 2 of 16