ላለፉት ሶስት ዓመታት የሣይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር በመሆን የሰሩት አቶ ደሴ ዳልኬ፤ የደቡብ ክልል ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳደር ሆነው እንደሚሾሙ ምንጮች ገለፁ፡፡ ላለፉት ስምንት ዓመታት የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር በመሆን ያገለገሉት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ከትላንት በስቲያ የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር በመሆን መሾማቸው የሚታወስ ሲሆን፤ እሳቸውን በመተካት አቶ ደሴ ዳልኬ የክልሉ ፕሬዚዳንት ሆነው ይሾማሉ ተብሏል፡፡

ባለፈው ሐሙስ በፓርላማ በተካሄደው የካቢኔ ሹመት ወ/ሮ ዳሚቱ ሐሚሳ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሆነው መሾማቸው ይታወቃል፡፡ በመጪው ሳምንት የደቡብ ክልል ምክር ቤት ጉባኤ የክልሉን ርዕሰ መስተዳደር ሹመት ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ባለፈው ሳምንት ከአስር በላይ የሚኒስትሮች ሹመት በፓርላማ መጽደቁ ይታወቃል፡፡

Published in ዜና

የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ ዋና ዳሬክተር አቶ ተፈሪ ፍቅሬና ሁለት ምክትል ዳይሬክተሮች በኪራይ ሰብሳቢነት ተገምግመው ከስራ ሃላፊነታቸው እንደተነሱ ተገለፀ፡፡
ተጠሪነቱ ለስራና ከተማ ልማት ሚኒስቴር የሆነው የቤቶች ኤጀንሲ ከትላንት በስቲያ ሶስቱን ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ከሥራ ሃላፊነታቸው ያነሳው በተለያየ ደረጃ ግምገማ ከተካሄደ በኋላ እንደሆነ ምንጮቻችን ገልፀዋል፡፡ የፀረ ሙስና ኮሚሽንም ከአንድ ዓመት በላይ በሥራ ሃላፊዎቹ ላይ ምርመራ ሲያደርግ እንደቆየ የጠቀሱ ምንጮች፤ ሃላፊዎቹ በኪራይ ሰብሳቢነትና ሃላፊነትን በአግባቡ ባለመወጣት ተገምግመው ነው ከሥራ ሃላፊነታቸው የተነሱት ብለዋል። ማተሚያ ቤት እስከገባንበት ሰዓት ድረስ በተነሱት ሃላፊዎች ምትክ ማን እንደሚሾም አልታወቀም፡፡

Published in ዜና
  • በፌስቡክ ላይ እርቃን ፎቶግራፍ መለጠፍ በህግ ያስቀጣል

 በ“ቢግ ብራዘር አፍሪካ” የሪያሊቲ ሾው ውድድር ላይ የተሳተፈችው የ26 ዓመቷ ኢትዮጵያዊት ቤተልሄም አበራ፤ በቅርቡ በተለያዩ ድረገፆች በተሰራጨው ቪዲዮ ላይ ወሲብ ስትፈጽም መታየቷ በወንጀል የሚያስከስሳት መሆኑን የገለፁ የህግ ባለሙያዎች፤ ፍ/ቤት የጥፋተኝነት ብይን ከወሰነባት የ5 ዓመት እስር እንደሚጠብቃት ተናገሩ፡፡ 

በወጣቷ ላይ ክስ ለመመስረት ዝግጅታቸውን እንዳጠናቀቁ ለአዲስ አድማስ የገለፁት የህግ ባለሙያዎቹ አቶ ጳውሎስ ተሰማ እና አቶ ተስፋሁን ፀጋዬ፤ ቤቲ የፈፀመችው ተግባር የህብረተሰቡን ባህል የሚቃረን በመሆኑና ይህም በሚዲያ በመተላለፉ በኢትዮጵያ ህግ ያስከስሳታል ብለዋል፡፡
እንኳን ድርጊቱን በአደባባይ የፈፀመ ቀርቶ ለመፈፀም ሙከራ ያደረገም በወንጀል እንደሚጠየቅ የገለፁት ጠበቆቹ፤ ቤቲ በአደባባይ የኢትዮጵያውያንን ባንዲራ ይዛ መልካም ገጽታችንን ማሳየት ሲገባት ባህላችን ሀይማኖታችንና ህጋችን የማይፈቅደውን ነገር በአደባባይ ፈጽማለች ብለዋል፡፡
ክሱን መመስረት ያስፈለገው ሌሎች በተመሳሳይ ተግባር ውስጥ የተዘፈቁ አካላትን ለማስተማር ታስቦ እንደሆነ ባለሙያዎቹ ተናግረዋል፡፡ እንደ ህግ ባለሙያነታቸው የማንም ውክልና ሳያስፈልጋቸው ክሱን በቅርቡ እንደሚመሰርቱና በወቅቱም በጉዳዩ ዙሪያ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጡ ባለሙያዎቹ አስታውቀዋል፡፡
እርቃን ምስሎችን በኢንተርኔት መለጠፍ በሕግ ያስከስሳል ብለዋል - ባለሙያዎቹ፡፡
ቤቲ የፈፀመችው ድርጊት በተለያዩ ድረ ገፆች መለቀቁን ተከትሎ ኢትዮጵያውያን በጉዳዩ ላይ ጐራ ለይተው በመደገፍና በመንቀፍ አስተያየታቸውን ሲሰጡበት የነበረ መሆኑን ያስታወሱት የህግ ባለሙያዎቹ፤ እኛ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ ስናስብ ምን አገባችሁ ያሉንም አሉ፤ እነዚህ ግለሰቦች ግን በህጉ መሠረት ይህን የማለት መብት የላቸውም ብለዋል። ለመልካም ፀባይ ተቃራኒ የሆኑ ድርጊቶችን መፈፀም ከ1 ዓመት እስከ 5 አመት በሚደርስ እስራት ሊያስቀጣ ይችላል ያሉት ባለሙያዎቹ፤ የቤቲ ጉዳይም እስከ 5 አመት እስር ሊያስቀጣ ይችላል ብለዋል፡፡
ዋናው አላማችን ቤቲን እንደማሳያ ወስደን እንዲህ አይነት ድርጊቶችም እንደሚያስቀጡ ለማሳየት ነው የሚሉት ጠበቆቹ፤ ዛሬ በፌስቡክና በተለያዩ የማህበራዊ ድረገፆች ላይ ሴቶች እርቃናቸውን ሆነው የተነሱትን ፎቶ እየለጠፉ መሆኑ ከዚህ የህግ ግንዛቤ ክፍተት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
“ከቢግ ብራዘር አፍሪካ” ውድድር የተባረረችው ቤቲ፤ በተለያዩ ሚዲያዎች በሰጠችው ቃለምልልስ፤ ድርጊቱን አለመፈፀሟንና የታየው ነገር ለውድድሩ አስፈላጊ በመሆኑ በትወና የተደረገ እንደሆነ ገልፃለች፡፡

Published in ዜና

“የማህበረ ስላሴ ዘደቂቀ ኤልያስ” አባላት፤ ከቅዱሳን አባቶች የተላክነውን የቅዱስ ኤልያስን መልዕክት ለአዲሱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክርስቲያን ፓትሪያሪክ አቡነ ማቲያስ እንዳናደርስ ተከለከልን አሉ፡፡ አርቲስት ጀማነሽ ሰለሞን የተካተተችበት መልዕክት አድራሽ ቡድን፤ ባለፈው ማክሰኞ ረፋዱ ላይ መልዕክታቸውን ጋዜጠኞች ባሉበት ለፓትርያርኩ ለማቅረብ ፓትሪያሪኩ ጽ/ቤት በር ላይ ተገኝተው የነበረ ቢሆንም የጥበቃ አባላት “ለማነጋገር ፍቃድ የላችሁም” ብለው መልሰዋቸዋል፡፡ ከማህበሩ አባላት መካከል አርቲስት ጀማነሽ ሰለሞን እና መ/ር ወልደመስቀል ፍቅረማርያም ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ ለሁለት ጊዜያት ያህል 4 ኪሎ በሚገኘው መንበረ ፓትሪያሪክ ጽ/ቤት በመሄድ ከአባቶች የተላኩትን መልዕክት ለማድረስ ቢሞክሩም ከጽ/ቤቱ የጥበቃ ሃላፊዎች ማለፍ አልቻሉም።

“በመጀመሪያው ቀን ከማህበረ ስላሴ መልዕክት ይዘን መምጣታችንን ለጥበቃዎች በመንገር ወደ ውስጥ እንድንገባ ከተፈቀደልን በኋላ ሌሎች በግቢ ውስጥ የነበሩ ጥበቃዎች በድጋሚ አስቁመውን ከስላሴ ካቴድራል ማኅበር የመጣችሁ መስሎን ነው እንጂ እናንተ መግባት አትችሉም በማለት ፓትሪያሪኩን እንዳናገኝ ተደርገናል” የሚሉት መ/ር ወልደመስቀል፤ በተለይ አንዲት ሴት የጥበቃ አባል ከአግባብ ውጭ ጀማነሽን እየገፈታተረች እንድትወጣ ማድረጓን ገልፀዋል፡፡ በሚዲያ ሳይቀር ቅዱስ ፓትሪያሪኩ ማንም ሰው ያለከልካይ በአካል መጥቶ ሊያነጋግረኝ ይችላል ያሉትን መነሻ አድርገን በመጀመሪያ ቀን ያለቀጠሮ የሄድን ቢሆንም ለሁለተኛ ጊዜ ቀጠሮ ለማስያዝ ብንፈልግም የሚያስተናግደን አካል በማጣታችን ለመመለስ ተገደናል የሚሉት መ/ር ወልደመስቀል፤ ጥበቃዎቹ የሄድንበትን ጉዳይ ጠይቀውን ከተረዱ በኋላ ፈጽሞ መግባት አትችሉም፤ ቀጠሮ ማስያዝ ከፈለጋችሁ አንድ እማሆይ አሉ፤ እሣቸውን አነጋግሩ ተባልን፤ የተባሉት ግለሰብ ግን ፍቃድ ወጥተዋል የሚል ምላሽ አገኘን ብለዋል፡፡ “አሁንም ለሶስተኛ ጊዜ ስንሄድ ጥበቃዎቹ ፈጽሞ መግባት አትችሉም፡፡ አካባቢውን ለቃችሁ ሂዱ አሉን” ብለዋል - የማህበሩ አባላት፡፡

ባለፈው ማክሰኞ 10 የሚደርሱ ሴቶችና ወንዶች የማህበሩ መገለጫ የሆነውን ነጭ ባለቀስተ ደመና ጥለት ልብስ ለብሰው ፓትሪያርኩ ጽ/ቤት በሩ ላይ ቆመው ነበር፡፡ የነብዩ ኤልያስ መልዕክት ምንድነው ብለን የጠየቅናት አርቲስት ጀማነሽ ሠለሞን “መልዕክቱ ለፓትሪያሪኩ ስለሆነ እሳቸው ከሰሙ በኋላ ለህዝብ እንድታደርሱ ይነገራችኋል” ብላለች፡፡ የመንበረ ፓትሪያሪክ ልዩ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታምሩ አበራ ከአዲስ አድማስ ስለ ጉዳዩ ማብራሪያ ተጠይቀው “እስካሁን ጥያቄ ያቀረበልን የለም፤ ቤተክርስቲያኒቷ የራሷ የቅሬታ አቀራረብ ሥርዓት አላት፡፡ ለቅሬታም ሆነ ለቡራኬ የሚመጡትን በቀጠሮ እናስተናግዳለን፡፡ እስከ ሀምሌ 21 ቅዱስ ፓትሪያሪኩን በስልክ ለማነጋገር የተያዙ ቀጠሮዎች አሉ” ብለዋል፡፡ ከነብዩ ኤልያስ መልዕክት አለን ያሉት ግለሰቦች “ኦርቶዶክስ” የሚለው ስያሜ “ለተንኮል” የገባ ስለሆነ የቤተክርስቲያኒቱ ስያሜ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መባሉ ቀርቶ “የኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን” መባል አለበት በሚል አላማ እንደሚንቀሳቀሱ ይታወቃል፡፡

Published in ዜና
  • ለኢኮኖሚው ግንባታ አሉታዊ አስተዋፅኦ እንዳለው ተገልጿል

 በተከታታይ ከፍተኛ እድገት እያስመዘገበ ነው በተባለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚወስደው ከግል ባለሃብቱ ኢንቨስትመንት ይልቅ የመንግስት ኢንቨስትመንት መሆኑን አንድ ጥናት ሰሞኑን ጠቆመ፡፡ 

ቀደም ሲል የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር እና በንግድ ሚኒስቴር የአለም ንግድ ድርጅት (WTO) ዋና አማካሪ የሆኑት አቶ ማሞ ምህረቱ ሰሞኑን በሂልተን ሆቴል “The investment Climate in Ethiopia; some reflections” በሚል ርዕስ ለምጣኔ ሃብት ባለሙያዎችና ለባለድርሻ አካላት ባቀረቡት ጥናት፤ እየተመዘገበ ባለው እድገት ውስጥ የግል ኢንቨስትመንቱ ሚና እየተዳከመ፣ በአንፃሩ የመንግስት ኢንቨስትመንት ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ ድርሻ እየያዘ መምጣቱን አስረድተዋል፡፡ እንደጥናት አቅራቢው፣ በ2011/12 ዓ.ም የአለም ባንክ ባወጣው ሪፖርት፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ8.5 በመቶ ማደጉን ያመለከተ ሲሆን በዚህ እድገት የመንግስት ኢንቨስትመንት 63 በመቶ ድርሻ ይዟል ተብሏል፡፡ የዓለም ባንክን ሪፖርት በመጥቀስ፣ ይህ አሃዝ ከሌሎች ሃገራት ጋር ሲነፃፀርም አገሪቱን ከአለም አገራት በመንግስት ኢንቨስትመንት ድርሻ በ3ኛ ደረጃ ያስቀምጣታል ብለዋል - ጥናት አቅራቢው፡፡
ለማሳየነት በተጠቀሰው የእድገት ዘመን በቱርኬሚስታን የመንግስት ኢንቨስትመንት ለአመታዊ ምርት እድገት (GDP) ያለው ድርሻ 38.6 በመቶ የነበረ ሲሆን አገሪቱን ከአለም ሃገራት በ1ኛ ደረጃ ያስቀምጣታል፣ ቀጥሎ ያለችው ኢኳቶሪያል ጊኒ ስትሆን መንግስት የ24.3 በመቶ ድርሻ አለው፤ በ3ኛ ደረጃ በምትከተለው ኢትዮጵያ ደግሞ የመንግስት ኢንቨስትመንት ለዓመታዊ ምርት እድገት ያለው ምጣኔ የ18.6 በመቶ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
የግል ኢንቨስትመንት ኢትዮጵያ ውስጥ በጣም ትንሽ መሆኑን የገለፁት ጥናት አቅራቢው፣እሱም ቢሆን ከአመት አመት እየቀነሰ በአንፃሩ የመንግስት ኢንቨስትመንት ሚና እየጎላ መጥቷል ብለዋል፡፡ ለመንግስት ኢንቨስትመንት መጨመር ማሳያ በማለት አጥኚው ሁለቱ አካላት ከባንክ የሚበደሩትን የብድር አቅም መጠን በማነፃፀር አቅርበዋል፡፡ በጥናት ውጤቱ ለማሳያነት በተጠቀሰው የ2011/12 አመት ከባንኮች በአጠቃላይ 224 ቢሊዮን ብር በብድር የተወሰደ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 57 በመቶውን የመንግስት የኢንቨስትመንት ድርጅቶች ሲወስዱ፣ 15 በመቶውን ብቻ የግል የኢንቨስትመንት ድርጅቶች ወስደዋል፡፡ መንግስት ከወሰደው ብድር 90 በመቶውን ያዋለው ለኢንቨስትመንት መሆኑም በጥናቱ ተመልክቷል፡፡
የግል ኢንቨስትመንቱ አሽቆልቁሎ የመንግስት እንዴት ሊጨምር ቻለ ለሚለው ጥናት አቅራቢው ምክንያት ያሏቸውን ነጥቦች የዘረዘሩ ሲሆን ከነዚህ መካከል የታክስ አስተዳደር ችግሮች፣ የመንግስት ኢንቨስትመንት መጠናከሩ፣የደንበኞች እጦት፣የሰው ሃይል አቅርቦት እጥረት፣ የሃይል እጥረት፣ የገንዘብ አቅርቦት፣ በመሰረተ ልማት ግንባታ ዘርፍ የግል ባለሃብቶች አለመጉላት እንዲሁም በየጊዜው ተለዋዋጭ ፖሊሲዎች መኖራቸው የሚሉት ይገኙበታል፡፡
የግል ኢንቨስትመንቱ መቀጨጭ ለኢኮኖሚ ግንባታው አሉታዊ አስተዋፅኦ እንዳለው የገለፁት አቶ ማሞ፤ መንግስት በቀጣይ የግል ባለሃብቱ ኢንቨስትመንት ድርሻ ጎልቶ እንዲወጣ ከፈለገ የተለያዩ ዘመናዊ አሰራሮችን መዘርጋት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ በዚህ ረገድ አዋጭ አሰራር በሚል ካቀረቡት መካከል፣ የኤሌክትሮኒክስ የአንድ መስኮት አገልግሎትን መጠቀም ይገኝበታል፡፡ ይህ አገልግሎት በአንድ የኮምፒውተር መስኮት ባለሃብቱ በተለያዩ የመንግስት መስሪያቤቶች ያሉትን ጉዳዮች ቢሮው ቁጭ ብሎ እንዲጨርስና ከተራዘመ የቢሮክራሲ ውጣ ውረድ እንዲድን ያደርገዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የታክስ ኮንፈረሶችን ማካሄድ፣ከግል ኢንቨስተሮች ጋር መወያየትና ችግሮችን አጥርቶ ማወቅ እንዲሁም የኤሌክትሪክና የመሳሰሉ የሃይል አቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት የኢንዱስትሪ ዞን ግንባታዎችን አጠናክሮ መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

Published in ዜና

“አዲስ ጉዳይ” መጽሔት በታፈኑ ዕውነቶች አምድ ላይ ለንባብ ባበቃው “ቀናት የሚታደጓቸው እድሜ ልኮች” የሚል ተንታኝ ሃተታ (ፊቸር ስቶሪ) የዓለም አቀፉን የጋዜጠኞች ማዕከል (ICFJ) የሁለተኛ ደረጃ ቀዳሚ ሽልማት አሸነፈ፡፡ ማዕከሉ ከአፍሪካ የጤና ጋዜጠኞች ማህበር እና ከአረብ ሚዲያ ፎረም ጋር በመተባበር ባዘጋጀው በክትባት ጉዳይ ላይ የሚያተኩር የዘገባ ውድድር ላይ 200 የእስያ፣ የአፍሪካና ስድስት የባህረሰላጤው አገራት ሚዲያዎች እንደተሳተፉ ታውቋል፡፡
መጽሔቱ በኢትዮጵያ የክትባት ተደራሽነት አናሳ መሆኑን አስመልክቶ የሰራው ተንታኝ ሃተታ፤ ከመላው አፍሪካ፣ ከእስያና ከባህረሰላጤው ሀገራት ሚዲያዎች ጋር ተወዳድሮ ነው ያሸነፈው፡፡
ከ14 ሀገራት በተውጣጡ በሙያው አንቱ በተባሉ ጋዜጠኞች በተዋቀረው ኮሚቴ በተሰጠው ዳኝነት ከ200 ዘገባዎች ውስጥ የአዲስ ጉዳይ “ቀናት የሚታደጓቸው እድሜ ልኮች” ከሁለተኛ ደረጃ ተሸላሚዎች የአንደኝነት ደረጃን ለማግኘት ችሏል፡፡
“ኢትዮጵያን ወክለን መወዳደራችንና ማሸነፋችን ዝግጅት ክፍሉን በጣም አስደስቶታል፡፡ በተለይም በአሁኑ ወቅት አዲስ ጉዳይን በአዲስ መልክ ለአንባቢያን ለማቅረብና በይዘቱ ላይ መጠነኛ ማሻሻያ አድርገን በባለሙያዎች የሚሰራ መጽሔት ለማድረግ ከልዩ ልዩ ዘርፎች ባለሙያዎችን እና አማካሪዎችን ቀጥረን እየተንቀሳቀስን ባለንበት ወቅት ይህ ውጤት መገኘቱ ሞራላችንን ገንብቶታል፡፡ ለበለጠ ስራም አነሳስቶናል” ብሏል የመጽሔቱ ዋና አዘጋጅ አቶ ዮሐንስ ካሳሁን፡፡
የውድድሩ ዋና አላማ በክትባት ማጣት ሳቢያ በየዓመቱ ህይወታቸውን የሚያጡ ህጻናትን ቁጥር ለመቀነስና ለከፍተኛ የአካል ጉዳት የሚዳረጉ ዜጐችን ጤና መታገድ የሚያስችል እውቀት መፍጠር ሲሆን የመጽሔቱ ዘገባ ኢትዮጵያ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ በማሳየት ህብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲኖረውና መንግስትም ክፍተቶቹን እንዲደፍን መረጃ የሚያስጨብጥ ነው ተብሏል፡፡
ቢሮውን ዋሽንግተን ዲሲ ያደረገው የአለምአቀፉ ጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ጆይስ ባርናታን አሸናፊዎቹ ይፋ በተደረጉበት ስነስርዓት ላይ እንደተናገሩት፤ “አሸናፊዎች ያቀረቧቸው ስራዎች እንደ ፖሊዮ ያሉ ከፍተኛ ጉዳት አድራሽ የሆኑ ነገር ግን በቀላሉ መከላከል የሚቻሉ በሽታዎችን መቋቋምና ማሸነፍ የሚቻልባቸውን መንገዶች ያመላከቱ ትምህርት ሰጪ ዘገባዎች ናቸው፡፡ ለህዝባቸው እና ለጤና ባለሙያዎቻቸው እንቅፋትን አስወግደው ስኬትን የሚያገኙባቸውን መንገዶችም የጠቆሙ ናቸው” ብለዋል፡፡
በውድድሩ አንደኛ የወጡት የናይጀሪያ “ቲቪሲ ኒውስ” ቴሌቪዥን ጣቢያ፣ የፓኪስታኑ “ኒውስ ዋን” ቴሌቪዥን ጣቢያ፣ የኮትዲቩዋሩ “አቬኑ 225 ኒውስ ሳይት” ድረገጽ እና የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች “ፊላንትሮፒ ኤጅ ማጋዚን” ሲሆኑ ጽሑፎቹ አንደኛ የወጡት ሚዲያዎቻቸው ሰፊ ተደራሽነት ያላቸው የቴሌቪዥን ኔትወርኮች በመሆናቸውና በኢንተርኔት ቴክኖሎጂ በታገዘ ስርጭታቸው አህጉራዊ ሽፋን በመፍጠራቸው መሆኑን የውድድሩ አዘጋጆቹ ተናግረዋል፡፡ ዋና አዘጋጁ አቶ ዮሐንስ እንዳለው፤ አዲስ ጉዳይ መጽሔት ከነዚህ ታዋቂ አህጉራዊ ሚዲያዎች ጋር ተወዳድሮ በ2ተኛ ደረጃ ተሸላሚነት ከተመረጡት የዩጋንዳው “ኤንቲቪ”፣ የፓኪስታኑ “ሳውዝ ኤሺያን ሜጋዚን”፣ እና የሳውዲአረቢያው “ሳውዲ ኒውስፔፐር ቱዴይ” ጋር የላቀ ውጤት በማስመዝገብ አንደኛ ደረጃ አግኝቷል፡፡ ይህ ውጤትም ኢትዮጵያውያን ሚዲያዎች በቴክኖሎጂ ቢታገዙና መልቲሚዲያ ቢሆኑ አህጉራዊ ተደራሽነትና ከየትኛውም አገር ጋር የሚፎካከር ሥራ መሥራት እንደሚችሉ ያመላከተ ነው፡፡

Published in ዜና
Page 13 of 13