“ሥራውን በሌሎች አሠራው፤ ምስጋናውን ግን አንተ ውሰድ”

ስመ ጥሩው ፈረንሳዊ ጦረኛ መሪ ናፖሊዮን ቦናፓርት፣ “ድል የአይታክቴ ሰዎች ናት” ሲል መናገሩን ታሪክ መዝግቦለታል፡፡ ልክ እንደ ናፖሊዮን ሁሉ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ፍራንክሊን ሩዝቬልትም “ከስኬት የሚያግደን ነገር በገሃዱ አለም የሚያጋጥመን እንቅፋት አይደለም፡፡ ይልቁንስ በአዕምሮአችን ውስጥ ስለ ችሎታችን ያለን የጥርጣሬ ሃሳብ ነው” በማለት እንደተናገሩ እስከ ዛሬ ድረስ ይጠቀስላቸዋል፡፡ የእነዚህ ታዋቂ መሪዎች ንግግር የያዘው መልእክት ጥልቅ ምርምር የሚያስፈልገው አይደለም - ቀላልና ግልጽ ነው፡፡ ንግግሮቹ የሰው ልጅ ልቡ ያሰበበት ቦታ ለመድረስና ከፍተኛ ስኬትን ለመጐናፀፍ፣ በከፍተኛ የራስ መተማመን ስሜት ያለመታከት ጠንክሮ መስራት እንዳለበት የሚያስገነዝቡ አባባሎች ናቸው፡፡

እንደ አብዛኛው የአለማችን ህብረተሰቦች፣ ይህን መልዕክት ለኮንጐ (ዛየር) ሰዎች ቢነግሯቸው፣ ሀሰት ነው ብለው አይከራከሩም፡፡ ነገር ግን “ኤሊ፣ ዝሆንና ጉማሬ” የተሰኘውን የሀገራቸውን እድሜ ጠገብ ተረት በመተረክ ከተጠቀሰው መልዕክት በተጨማሪ የሰውን ልጅ ወደ አለመው ግብ አድርሶ ስኬትን የሚያጐናጽፍ አንድ ሌላ ዘዴ ወይም መንገድ እንደሚያውቁ ሊናገሩ ይችላሉ፡፡ ተረቱ የሚተርከው፣ እሱ መስራት የሚገባውን ስራ፣ ዝሆንና ጉማሬን በማሰራት ያለመውን ግብ መምታትና ስኬትን መጐናፀፍ ስለቻለው ኤሊ ነው፡፡ ኮንጐአውያን በዚህ ተረት አማካኝነት የሚያስተላልፉት የስኬት ዘዴ ወይም መንገድ “ለስኬትህ የሚያስፈልገውን ስራ ሁሉ ሌሎች እንዲሰሩልህ አድርግ፡፡ ስኬቱን ግን አንተው ብቻ ተጐናፀፍ” የሚል ነው፡፡ ይህን ግልጽ ለማድረግ የቀረበው ማብራሪያ ደግሞ እንዲህ ይላል - “አላማና እቅድህን ከግቡ ለማድረስ የሌሎች ሰዎችን ጥበብና ችሎታ፣ ክህሎትና ጉልበት ሳታመነታ ተጠቀም፡፡ ይህን ማድረግህ እጅግ በጣም ጠቃሚ የሆነውን ጊዜህንና ጉልበትህን መቆጠብ ብቻ ሳይሆን አማልዕክቶች ብቻ እንዳላቸው አይነት ጥራትና ፍጥነት እንዲኖርህ ያደርግሃል፡፡

ይህም ሌሎች ሰዎች ጨርሶ የሌላቸውን ልዩ ግርማ ሞገስ ያጐናጽፍሃል፣ የማታ ማታም ስራውን የሰሩልህ ሰዎች ወዲያውኑ ሲረሱ፣ አንተ ግን ሁሌም እየታወስክና ስምህ በስኬት እየተጠራ ትኖራለህ፡፡ እናም ሌሎች ሰዎች ላንተ ሊሰሩልህ የሚችሉትን ስራ አንተ በፍፁም አትስራ፡፡” ይህ የስኬት መንገድና ማብራሪያው ከመጀመሪያዎቹ የናፖሊዮንና የሩዝቬልት መንገዶች ጋር ሲነፃፀር፣ የስነምግባር ክርክር እንደሚያስነሳ ቅንጣት አያጠራጥርም፡፡ የዚያኑ ያህልም ሰዎች ስኬትን ለመጐናፀፍ ባደረጉት ጥረት ውስጥ ይህኛውንም ዘዴ በመጠቀም የተመኙትን ስኬት መጐናፀፍ እንደቻሉ ጨርሶ መካድ አይቻልም፡፡ በአለማችን በተለያየ የሙያ ዘርፍ ከፍተኛ ስኬትን በመቀዳጀት ታላቅ ዝናና ፀጋ የተጐናፀፉ ሰዎች፣ የህይወት ታሪክ የተፃፈበትን መዝገብ በጥሞና ብንመረምር፣ በአንዱ ወይም በሌላኛው ምዕራፍ ውስጥ ኮንጐአውያን በተረታቸው በጠቀሱት የስኬት ጐዳና የተጓዙ በርካቶች እንዳሉ ማረጋገጥ እንችላለን፡፡ አለማችን ከቶማስ ኤዲሰን የበለጠ እጅግ በርካታ የፈጠራ ውጤቶችን ሊያበረክትላት የቻለ ሌላ የፈጠራ ባለሙያ እስከዛሬ ድረስ ጨርሶ አላገኘችም፡፡ የካቲት 11 ቀን 1847 ዓ.ም በኦሀዮ ግዛት የተወለደው አሜሪካዊው ቶማስ አልቫ ኤዲሰን፣ በህይወት በቆየበት ሰማኒያ አራት አመታት ውስጥ አንድ ሺ ዘጠና ሶስት የፈጠራ ውጤቶችን የፈጠራ መብት (Patent) በስሙ በማስመዝገብ፣ የአለምን ሬከርድ እስካሁንም ድረስ የጨበጠ የፈጠራ ሰው ነው፡፡

በዚህም የተነሳ ከፍተኛ ስኬትንና አለማቀፋዊ ዝናን መጐናፀፍ ችሏል፡፡ በስሙ ያስመዘገባቸውን እነዚያን ሁሉ የፈጠራ ውጤቶች በስራ ላይ እንዲውሉ ባያደርግ ኖሮ፣ አለማችን የዛሬዋን አለም እንደማትሆን መገመት አያዳግትም፡፡ ለምሳሌ የኤሌክትሪክ አምፑልን እሱ ባይሰራው ኖሮ፣ የአዳምን ዘር ማን ከኩራዝ ጭስ ይገላግለው እንደነበር በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡ በአለማችን የመጀመሪያ የሆነውን የኢንዱስትሪ ምርምር ላቦራቶሪ ያቋቋመውም ቶማስ ኤዲሰን ነበር፡፡ በ1880ዎቹ አመታት ሰርብያውያን “እንዲያው መጨረሻውን ሳያሳየን አይግደለን” እያሉ ለአምላካቸው ስለት የሚቋጥሩለት እንደ ኒኮላ ቴስላ ያለ ወጣት ሳይንቲስት አልነበራቸውም፡፡ ያኔ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰርቢያውያን፣ ወጣቱ ኒኮላ ቴስላ ድንቅ የፈጠራ ውጤቶችን በመስራት፣ እነሱንና ሀገራቸውን በድፍን አለሙ ዘንድ ለዝንተ አለም ሲያስጠራ ይኖራል ብለው በእጅጉ ይተማመኑበት ነበር፡፡ ሰርቢያውያን ኒኮላ ቴስላን እንዲህ ቢተማመኑበት በእርግጥም እውነታቸውን ነበር፡፡ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቄስ ከነበሩት አባቱና የቤት እመቤት ከሆኑት እናቱ ሰኔ 10 ቀን 1856 ዓ.ም በዛሬዋ ክሮኤሽያ ውስጥ የተወለደው ቴስላ፤ የላቀ አስተሳሰብና ከፍተኛ የፈጠራ ችሎታ ባለቤት መሆኑን ያስመሰከረው ገና የአንደኛ ደረጃ ተማሪ ሳለ ነው፡፡ ኒኮላ ቴስላ ከዚህ በተጨማሪም ቀላል የማይባል የግጥም ችሎታ ነበረው፡፡

ኦስትሪያ ግራዝ ከተማ ከሚገኘው የቴክኒክ ዩኒቨርሲቲና ፕራግ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የኢንጂነሪንግ ትምህርቱን ከጨረሰ በኋላ የ “Rotating Magnetic field” ን ግኝት በማግኘት የፈጠራ ባለቤትነቱን በስሙ በማስመዝገብ፣የፈጠራ ችሎታውን አሀዱ ብሎ ለመላው አለም ማሳየት ችሏል፡፡ በመቀጠልም ባለ ሶስት ፌዝ የኤሌክትሪክ ሃይል ማስተላለፊያ ሲስተም፣ የኤሌክትሪክ ሞተሮችና፣ ትራንስፎርመሮችን በመስራት ሰርቢያውያንን አጀብ አስባላቸው፡፡ በአለምአቀፉ የኤዲሰን ኩባንያ የፓሪስ ቅርንጫፍ ውስጥ ተቀጥሮ መስራት ከጀመረበት ከ1882 ዓ.ም ጀምሮ አብረውት ይሰሩ የነበሩ ባልደረቦቹም ቴስላ ልዩ የሆነ የአስተሳሰብና የፈጠራ ችሎታ እንዳለው በግልጽ ይመሰክሩለት ነበር፡፡ በተለይ ይሰራበት የነበረው የኤዲሰን ኩባንያ የፓሪስ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጁና የቶማስ ኤዲሰን የቅርብ ጓደኛ የነበሩት ቻርለስ ባችለር፣ የወጣቱ ሰርቢያዊ ሳይንቲስት የኒኮላ ቴስላ የምር አድናቂ ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ ቻርለስ ባችለር፣ ቴስላ ሙሉ ችሎታውን አውጥቶ ለመጠቀም በወቅቱ አውሮፓ የምትመች ቦታ አይደለችም ብለው ያምኑ ነበር፡፡ እናም ፓሪስን ለቆ ለሳይንቲስቶችና ለፈጠራ ባለሙያዎች በእጅጉ የምትመች ሀገር ናት ወደሚሏት አሜሪካ ለመሄድ ፈቃደኛ ከሆነ፣ ከቶማስ ኤዲሰን ጋር እንዲገናኝና የፈጠራና የምርምር ስራዎቹን እውን እንዲያደርግ የሚያስፈልገውን እገዛ ሁሉ እንዲያገኝ እንደሚያደርጉለት ደጋግመው ቃል ይገቡለት ነበር፡፡

ኒኮላ ቴስላም በ1883 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ቻርለስ ባችለር የፃፉለትን ደብዳቤ ተቀብሎ፣ የእድል እጣ ፈንታውን ለመሞከር በመወሰን ወደ አሜሪካ አቀና፡፡ ሰርቢያውያን ብዙ ነገር እንደሚሰራላቸው የተማመኑበት ወጣቱ ሳይንቲስታቸው ፈረንሳይን ለቆ አሜሪካ የመግባቱን ዜና ሲሰሙ፣ ልጃቸው ከእንግዲህ በኋላ የአሜሪካ እንጂ የእነሱ ልጅ እንደማይሆን በመገመት ልባቸው በሀዘን ተሰበረ፡፡ ፀጉረ ልውጡ ሰርቢያዊ ወጣት ሳይንቲስት ኒኮላ ቴስላም ለወራት እጅግ አሰልቺ የሆነ የመርከብ ጉዞ ካደረገ በኋላ በ1884 ዓ.ም መባቻ ላይ አሜሪካ ኒውዮርክ ደርሶ ከዝነኛው የፈጠራ ሰው ከቶማስ ኤዲሰን ጋር ተገናኘ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ አንድን ሰው በአስተማማኝና በማያዳግም ሁኔታ ለማስተዋወቅ ቁንጅናንና ዝናን የሚያስንቅ የማስታወቂያ ዘዴ እስከዛሬ ድረስም ጨርሶ አልተፈጠረም፡፡ ኒኮላ ቴስላም ይህንን በሚገባ ተገንዝቧል፡፡ ስለዚህ ከዚህ በፊት በአካል አይቶት ከማያውቀው ቶማስ ኤዲሰን ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ሲገናኙ “ለመሆኑ አንተ ማነህ?” ብሎ መጠየቅ አልፈለገም፡፡ ጓደኛው ቻርለስ ባችለር፣ ከዚህ በፊት ከላከለት የተለያዩ መረጃዎች የኒኮላ ቴስላን ማንነት በሚገባ የተረዳው ቶማስ ኤዲሰንም ስለጉዞው ሁኔታ ካቀረበለት አንዳንድ ተራ ጥያቄዎች በቀር ሌላ አላስቸገረውም፡፡ ወዲያውኑም ኒኮላ ቴስላ፣ ቻርለስ ባችለር ጽፈው የሰጡትን ደብዳቤ ለኤዲሰን ሰጠው፡፡ ኤዲሰን ደብዳቤውን አንብቦ ከጨረሰ በኋላ የቴስላን ጀርባ በእጁ መታ መታ በማድረግ፣ በዲናሞ ላይ የሚያደርገውን ምርምር ጠንክሮ እንዲገፋበት ካበረታታው በኋላ ማናቸውንም አይነት እርዳታ ከፈለገ፣ ያለ አንዳች ማመንታት እንደሚያደርግለት አስረዳው፡፡ ቶማስ ኤዲሰን፣ ዘመናዊ ዲናሞ ለመስራት አስቦ የጀመረውና ከሶስት አመት በላይ ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም ሊሳካለት ባለመቻሉ ተስፋ ቆርጦ ያቆመው ትልቅ የፈጠራ ፕሮጀክት ነበረው፡፡

ስለዚህ ፕሮጀክት ባሰበ ቁጥርም ከልቡ ይቆጭ ነበር፡፡ በዚህ ረገድ ከፍተኛ እውቀት ያለው ኒኮላ ቴስላን በምርምር ስራው እንዲገፋበት ቀድሞ ያበረታታውም፣ አቅቶት የተወውን ዲናሞ አሻሽሎ ሊሠራው ይችላል ብሎ በማሰቡ ነበር፡፡ ይህ ሃሳቡና እቅዱ እንዲሳካ ከሁሉ በፊት ምን ማድረግ እንዳለበት በሚገባ የተረዳው ኤዲሰን፤ ኒኮላ ቴስላ ፈቃደኛ ከሆነ በዓለም አቀፉ የኤዲሰን ኩባንያ ዋና መስሪያ ቤት በሳይንቲስትነት ተቀጥሮ መስራት እንደሚችል ግብዣውን በትህትና አቀረበለት፡፡ ቴስላም ኤዲሰን ያቀረበለትን ይህን የስራ ጥያቄ ለአፍታም እንኳ ሳያመነታ ወዲያውኑ ተቀበለ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ቴስላ ሊያመነታ የሚችልበት አንዳችም ምክንያት አልነበረውም፡፡ ምክንያቱም ከፈረንሳይ ፓሪስ ተነስቶ አሜሪካ ኒውዮርክ ሲገባ፤ በኪሱ ውስጥ የነበረው አራት ሳንቲም፣ መርከብ ውስጥ በጉዞ ላይ እያለ የፃፋቸው የተወሰኑ ግጥሞችና በአየር ላይ የሚበር ማሽን ለመስራት አስቦ የሂሳብ ቀመርና ስሌት የሰራባቸው ቁርጥራጭ ወረቀቶች ብቻ ነበር፡፡ ቴስላ ከተቀጠረ በኋላ የኤዲሰን “የግል ቤተ መቅደስ” እየተባለ በሰራተኞቹ ዘንድ በሚጠራው ልዩ ወርክሾፕ ውስጥ ከኤዲሰን ጋር መስራት ጀመረ፡፡ ከእለታት ባንዱ ቀንም በወርክሾፑ አንድ ጥግ ላይ የተቀመጠ ጥንታዊ አሰራር ያለው ዲናሞ ተመለከተ፡፡

ዲናሞው ኤዲሰን በዘመናዊ ሁኔታ አሻሽሎ ለመስራት ፈልጐ፤ ከሶስት አመት በላይ ሞክሮ ሳይሳካለት ሲቀር በተስፋ መቁረጥ የተወው ዲናሞ ነበር፡፡ ቴስላ ዲናሞውን አንስቶ እያገላበጠ አሰራሩን በደንብ መፈተሽ እንደጀመረ ድንገት ከኤዲሰን ጋር ተገጣጠሙ፡፡ ቴስላ በዲሞው ላይ ያሳየውን ከፍተኛ ትኩረት በሚገባ ያስተዋለው ኤዲሰን፤ “ስሪቱን ላሻሽለው ፈልጌ በጊዜ ማጣት ምክንያት ብዙም ትኩረት ያልሰጠሁት ዲናሞ ነው፡፡ የሚረባ ነገር ስላልሆነ አንተ በራስህ ምርምር ላይ አተኩር እንጂ ለዚህ ጊዜህን ልታጠፋበት አይገባም፡፡” ብሎት መልስ ሳይጠብቅ ወደ ቢሮው አመራ፡፡ ቴስላ ግን ኤዲሰንን ተከትሎት ሄደና “ቶማስ አንዴ አዳምጠኝ፡፡ ምን መሰለህ-- ዲናሞው የማይረባ ነው አይባልም፡፡ እኔ በዘመናዊ መልክ አሻሽዬ ልሰራው እችላለሁ፡፡” አለው፤ እርግጠኝነት በተሞላው ስሜት፡፡ የኤዲሰን ልብ በደስታ ዘለለ፡፡ ያጠመደው ወጥመድ በቀላሉ ያዘለት፡፡ እርሱ መስራት ያልቻለውን ስራ አሁን ሌላ ሰው ሊሠራለት ነው፡፡

ይህ ደግሞ ከምንም ነገር በላይ ለኤዲሰን በጣም አስፈላጊና አስደሳች ነገር ነው፡፡ ይሁን እንጂ እቅዱ እስከ መጨረሻው ድረስ ግቡን መምታት ስላለበት፣ የተሰማውን ከፍተኛ የደስታ ስሜት በውስጡ አፍኖ በመያዝ፣ አሁንም ምንም አይነት ትኩረት እንዳልሰጠው በሚያሳይ ሁኔታ “እየውልህ ቴስላ--- እንደ እኔ ከሆነ በዚህ ውዳቂ ዲናሞ ላይ ምንም አይነት ጊዜህንም ሆነ ጉልበትህን ባታባክን እመርጣለሁ፡፡ ግዴለም ይሁን ብለህ ከገፋህበትና አሻሽለህ ከሰራኸው ግን የሃምሳ ሺ ዶላር ሽልማት እሰጥሃለሁ፡፡ የፈጠራ መብት ባለቤትነት መብቱንም ትወስዳለህ፡፡” አለው፡፡ ቴስላ እንዲህ ያለ ታላቅ ሽልማት (የያኔው ሃምሳ ሺ ዶላር በዛሬው ተመን ከግማሽ ሚሊዮን ዶላር ይበልጣል) ይዘጋጅልኛል ብሎ ጨርሶ ያልገመተው ነገር ስነለበር፣ በደስታ እየፈነጠዘ ወደ ወርክሾፑ ተመለሰ፡፡ ቶማስ ኤዲሰን፤ ቴስላ ከቢሮው እንደወጣ እግሮቹን ጠረጴዛው ላይ ዘርግቶ ወደ ኋላው ተለጥጦ ቁጭ አለና፣ በከፍተኛ የእርካታ ስሜት በረጅሙ ተነፈሰ፡፡ ቴስላ ዲናሞውን እንደሚያሻሽለው እርግጠኛ ስለነበር “ከሶስት አመት በላይ ደክሜ መና ቀርቼበት የነበረውን ትልቅ ፕሮጀክቴን ያለ አንዳች ተጨማሪ ጊዜና ድካም፣ ከቦርሳ ቢወድቁ እንኳ በማይታወቁ ጥቂት ዶላሮች ብቻ ማሳካት መቻል በእውነቱ በጣም፣ እጅግ በጣም ጥሩ ነገር ነው፡፡” አለና ለብቻው ፈገግ አለ፡፡ ኒኮላ ቴስላ የተዘጋጀለት ሽልማት ከተነገረው በኋላ፣ በቀን አስራ ስምንት ሰአት እየሰራ፣ ለአንድ አመት ያህል የተለያዩ ሙከራዎችን ሲያካሂድ ከቆየ በኋላ፣ ዲናሞውን በላቀና በዘመናዊ ሁኔታ አሻሽሎ ለመስራት ቻለ፡፡

ወዲያውኑም የተዘጋጀለትን የሃምሳ ሺ ዶላር ሽልማት ለመቀበል በከፍተኛ የእርካታና የአሸናፊነት ስሜት ተሞልቶ፣ የስኬት ዜናውን ለኤዲሰን አበሰረው፡፡ ኤዲሰን ምንም እንኳ በእርግጠኝነት የጠበቀው ቢሆንም የስኬቱን ብስራት እንደሰማ፣ ቴስላን በአድናቆት አቅፎ ወደ ላይ አነሳውና “ብራቮ!ብራቮ!ብራቮ ቴስላ! እጅግ የሚያስደንቅ ነገር ነው የሰራኸው፡፡ ስለዚህ የአንድ መቶ ሃምሳ ዶላር የደመወዝ ጭማሪ እንዲደረግልህ ለሰራተኛ አስተዳዳሪው አሁኑኑ ትዕዛዝ እሰጥልሃለሁ” አለው፡፡ ቴስላ ይህን የደመወዝ ጭማሪ እንደ ሌላ ሽልማት ወይም ተጨማሪ ልዩ ማበረታቻ እንደተደረገለት በመቁጠር በከፍተኛ የደስታ ስሜት የኤዲሰንን ቀኝ እጅ በሁለት እጆቹ ጥብቅ አድርጐ ያዘና “ቶማስ! በጣም አመሰግናለሁ! በእውነት በጣም አመሰግንሃለሁ! አንተ መልካም ሰው ነህ! የሃምሳ ሺ ዶላር ሽልማቱ በራሱ እኮ ማንም በቀላሉ የማያገኘው ትልቅ ሽልማት ነው፡፡ በዚህ ላይ የአንድ መቶ ሃምሳ ዶላር የደመወዝ ጭማሪ ሲታከልበት ዋው! ይህ መቼም ህልም ህልም የሚመስል በጣም ድንቅ ነገር ነው፡፡” አለው፡፡ “ኦህ! ሽልማቱ? ሃምሳ ሺ ዶላሩ?” ኤዲሰን ከት ብሎ ሳቀ፡፡

ከተቀመጠበት ተነስቶ ቴስላን ትከሻውን አቀፈውና “አይ ቴስላ! ለካ እስከዛሬ ድረስ የእኛ የአሜሪካኖች ቀልድ አይገባህምና! ሃምሳ ሺ ዶላር ትሸለማለህ ያልኩህ እኮ የቀልዴን ነበር--- አንተ የእውነቴን መስሎህ ነበር እንዴ? አዬ እንዲያው የሰው ሀገር ሰው መሆን ለካ ችግር ነው አቦ!” አለው፡፡ ኒኮላ ቴስላ ተስፋ አድርጐት የነበረው ነገር እንደ ጉም በኖ እንደጠፋ ገባውና ሃይለኛ የንዴት ስሜት ሰውነቱን ሲወረው ተሰማው፡፡ አፉን ደም ደም አለው፡፡ ነገር ግን ስሜቱን እንደ ምንም ተቆጣጥሮ ከኤዲሰን ቢሮ ወጣና በቀጥታ ወደ ቤቱ አመራ፡፡ ለአስራ አራት ቀናት ስራ ሳይገባ ቤቱ ተቀምጦ ግጥም በመፃፍ የተጐዳ ስሜቱን ለመጠገን ሞከረ፡፡ በአስራ አምስተኛው ቀን ኤዲሰንን በድጋሚ ለማነጋገር ፈልጐ ወደ ቢሮው ሄደ፡፡ ኤዲሰን ቴስላን እንዳየው ወደ እርሱ ተንደርድሮ ሄደና “ቴስላ በደህናህ ነው እንዲህ የጠፋኸው? የሰራተኛ አስተዳዳሪው የአንድ መቶ ሃምሳ ዶላር የደመወዝ ጭማሪ እንደተደረገልህ የሚገልፀውን ደብዳቤ ሊሰጥህና በዚያውም እንኳን ደስ ያለህ ሊልህ ፈልጐ ከየት ያግኝህ? እኔማ ክፉ ነገር አጋጥሞህ እንዳይሆን ብዬ በጣም ሰግቼ ነበር፡፡ ደህና ከሆንክ በጣም ጥሩ ነገር ነው፡፡

እንግዲህ ዛሬ በሰላም ከተገናኘን በእውነቱ ለሰራኸው ምርጥ ስራ እንኳን ደስ ያለህ ልልህ እወዳለሁ፣ ይሄውልህ ቴስላ የአሜሪካ የፓተንት ቢሮ አሻሽለህ የሰራኸውን (Induction motor) ዲናሞ ባጭር ጊዜ ውስጥ መርምሮ ፓተንቱን አጽድቆና መዝግቦ ልኮልናል፡፡” አለውና በመስታወት ፍሬም ውስጥ የተቀመጠ የፈጠራ ውጤት ባለቤትነት መብት ሰርቲፊኬት አሳየው፡፡ በፈጠራ ባለቤትነት የተመዘገበው ቶማስ አልቫ ኤዲሰን ብቻ ነበር፡፡ የቴስላ አንጀት በሀዘን ተኮማተረ፣ ጭንቅላቱ በንዴት ክፉኛ ጋለበት፡፡ መላ ሰውነቱ በቁጣ ግሎ እጁ እንደ አንዳች ነገር ተንቀጠቀጠበት፡፡ ግን ሁሉንም ነገር በውስጡ ዋጥ አደረገና አንዲትም ቃል ሳይተነፍስ በመጣበት ሁኔታ ወደ ቤቱ ተመለሰ፡፡ ይህም “ከዝነኛው የፈጠራ ሰው” ቶማስ አልቫ ኤዲሰን ጋር የመጨረሻው ግንኙነቱ ሆነ፡፡ ኒኮላ ቴስላ፣ ሳይንስ በተረጋገጠ እውነት ላይ የሚያተኩር ሙያ ስለሆነ የተቀረውን አለም ከሚያውከው ተራ ፉክክር የራቀ ነው ብሎ የሚያምን ሰው እንደነበር በቅርብ የሚያውቁት ይመሰክራሉ፡፡ ቶማስ ኤዲሰን ደግሞ የቴስላ ተቃራኒ ነበር፡፡ ስራውንና የህይወት ጉዞውን በቅርብ የመረመሩ አጥኝዎች፣ ኤዲሰን ከሳይንሳዊ ሃሳብ አፍላቂነቱና ከፈጠራ ባለሙያነቱ ይልቅ መልካም አጋጣሚዎችን ለይቶ በማወቅና ሌሎች የላቁ ባለሙያዎችን ቀጥሮ የሚፈልገውን ነገር በማሰራት፣ መጠቀምን አሳምሮ የሚያውቅ፣ እሳት የላሰ ነጋዴ ነው ይሉታል፡፡

ለነገሩ እሱም ይህን አልደበቀም፡፡ ስለዚህ ጉዳይ በ1889 ዓ.ም ተጠይቆ “አለም አጀብ ያለለትን የሂሳብ ሊቅ መቅጠር እየቻልኩ፣ የግድ የሂሳብ አዋቂ ካልሆንኩ ብዬ ምን ያዳርቀኛል?” በማለት መልስ ሰጥቷል፡፡ ቶማስ ኤዲሰን የሌሎችን የፈጠራ ውጤት አላግባብ ትወስዳለህ ተብሎ በ1982 ዓ.ም ለተጠየቀው ጥያቄ የሰጠው መልስ ግን በጣም አስገራሚ ነበር፡፡ “በንግድና በኢንዱስትሪ መስክ ሁሉም ሰው ይሰርቃል፤ እኔም ብዙ ነገሮችን ከሌሎች ሰርቄአለሁ፡፡ እንዴት፣ ምንና መቼ መስረቅ እንዳለብኝ ግን አሳምሬ አውቃለሁ፡፡” ነበር ያለው፡፡ ቶማስ ኤዲሰን እንዲህ ያለ መልስ መስጠቱ አስገራሚ ነው የተባለው፣ ሁሉም ሰው እንደሚሰርቀው እኔም እሰርቃለሁ በማለቱ አይደለም፡፡ ይህንንማ ማን ይክዳል! ይልቁንስ አስገራሚው ነገር ታላቅ ለሆነው ክቡሩና ዝነኝነቱ ሳይጨነቅ፣ እውነቱን አምኖ በራሱ አንደበት ደፍሮ መናገር መቻሉ ነበር፡፡ ዝነኛው የፊዚክስ ሊቅ ሰር አይዛክ ኒውተን፣ ከረጅም ዓመታት በፊት ለተመሳሳይ ጥያቄ የሰጠው መልስም “ዋናው ቁም ነገርና እኔም በተግባር ያደረግሁት፣ ከታላላቅና ድንቅ ጠቢባን ትከሻ ላይ መቆም ነው፡፡” የሚል ነበር፡፡

የሆኖ ሆኖ ቶማስ ኤዲሰን፣ ወጣቱን ሰርቢያዊ ሳይንቲስት ኒኮላ ቴስላን (በ1891 ዓ.ም የአሜሪካን ዜግነት ከተቀበለ በኋላ የሚጠራው ሰርቢያ አሜሪካዊ ወይም ትውልደ ሰርቢያ አሜሪካዊ እየተባለ ነው) እንደምን አድርጐ እንደተጠቀመበትና የማይፈጽመውን ቃል እየገባ “እንዳታለለው” በርካታ አሜሪካዊ ሳይንቲስቶች በሚገባ ያውቁ ነበርና፣ በ1917 ዓ.ም የአሜሪካ የኤሌክትሪክ መሀንዲሶች ተቋም አመታዊው “የኤዲሰን ሜዳሊያ” በወቅቱ የድህነት ኑሮ ይገፋ ለነበረው ኒኮላ ቴስላ እንዲሰጥ በአንድ ድምጽ ወሰነ፡፡ ይህንን ዜና የሰማው ኒኮላ ቴስላም የሚከተለውን ደብዳቤ ለተቋሙ በመፃፍ ሜዳሊያውን እንደማይቀበል አስታወቀ፡፡ “የተቋማችሁ ዋነኛው ህልውና የተመሰረተበትን አዕምሮዬንና የአዕምሮዬን የፈጠራ ውጤቶች እውቅና መስጠት ከልክላችሁኝ እንድራብ ካደረጋችሁኝ በኋላ፣ በተቋማችሁ አባላት ፊት ኮቴ ላይ አንጠልጥዬ እንድንጐራደድ፣ ባዶ ሰውነቴን በሜዳሊያ ለማስጌጥ መወሰናችሁ ከቶ እንደ ምን ያለ ቀልድና ምን የሚሉት ፌዝ ነው?”

Saturday, 20 July 2013 10:34

ዘቢብ

(የሰባ መስዋዕት)

ሐበሻ ሽፍታ ይወዳል፡፡
በዝምታ የተኳለ መልከመልካምነት አይመስጠውም፡፡
የቁጣ ዝናሬን ታጥቄ…ምንሽሬን ወልውዬ…ግስላ መሆን ነው፡፡
የገዛ ህሊናው ነበር እንዲህ እያለ ልቡ ውስጥ ነጋሪት እየጐሰመ ፋኖ ያደረገው፡፡
እንየው፤ ቀጠሮው ቀፎታል፡፡
የልጅነት ጊዜውን በዘርዛራ ወንፊት አንገዋሎ፣ አንገዋሎ፣ የትዝታውን ውጤት እንቅጥቃጭ አድርጐበታል፡፡
እጁ ላይ “ቴስቲ” የሆነ ነገር ነበረው፡፡
ኩርፊያ ስመጥሩ ጥል መሆን የለበትም ባይ ነው፡፡ ግን የታጠቀውን የኩርፊያ ድግ መተርተር አልቻለም፡፡ በልብ አቂሞ ትዳር መምራት ከንቱነት ነው፡፡ ሐገርንም እንደዛው፡፡
በዛች የጐሽ ግምባር በምታክል ቤት ውስጥ …ከመጠን በላይ ተንጐራደደ …እስኪያልበው…የፍርሃቱን ግዳይ ለመጣል ይመስል፡፡ ይወራጫል፣ ፀጉሩን ይነጫል፣ እጁን በቡጢ ይነርታል…የገዛ ራሱን ምን ፍጠር እንደሚለው አይታወቅም፡፡
ጠረጴዛው ጫፍ ላይ የተቀመጠው የውኃ መጠጫ ብርጭቆ፣ የተወለወለው ወለል ላይ “ዋይ” ብሎ ላመ፡፡ “መጪው ጊዜዬ ይሄ ይሆን…” ተጨነቀ፡
እንደ ውኃ የፈሰሰውን ብርጭቆ ለመሰብሰብ አልፈለገም፡፡ የከበረ መዋረድ ስለሌለ …በገዛ እጁ ውዱን ፈትቶ ለቋል…አርዝሞ ማሰር… አለችኝ ብሎ ለመኩራራትም ሆነ ለመኮፈስ አያስደፍርም፡፡
ሴት ልጅ አፍቅራው ከልቡ ደጅ ተመላልሳ፣ ሳያስበው የራቀችው ወንድ ሲባንን እሱ…የወፍጮ ቤት ጣራና ግድግዳ ነው፡፡ በተሰጠው ልክ መስጠት ካቃተው…ባዶነቱን መሙያ ዘመኑን ሙሉ ኳታኝ ነው፡፡ መሐል ላይ ገመዱ የተጠመጠመበት ስፍራ መልኩን ቀይሮ ወደነበረበት ለመመለስ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ ብዙ ውዶች…ዋጋ ያስከፍላሉ!
በአፍ መጠን የሚጐረስ የፍቅር ጉርሻ ከልብ ሆድ መድረሱ፣ በእጅ ምጣኔና ልኬት ላይ ተወስኖ ይኖራል፡፡ “የትም አይሄድም” ያልነውና የተመጻደቅንበት ፍቅርም ሆነ ሌላ ነገር ሳናስበው ባልተረዳነው አኳኋን ካጠገባችን ይርቃል፡፡
ፈትቶ መልቀቅም፣ አስረዝሞ ማሰርም፣ ሁለቱም ከጥርጣሬ ድር የተሰራ አንድ አለኝነት ነው፡፡
እንየው፤ በቅጡ ያልተረዳው ሥጋት ከመጠን በላይ ሲጮህ ጆሮው ውስጥ ይሰማዋል፡፡ ተረብሿል፡፡
አይኑ እምባ ማቅረሩን ያስተዋለው…የመስኮቱን መጋረጃ መንጭቆ ሲገልጠው ነው፡፡ የገዛ ፊቱን ተጠራጥሮ ተመለከተው…በእንዲህ አይነት ስሜት ውስጥ ፊቱ የተቃጠለ ከተማ ነው የሚመስለው፡፡ ከንፈሩን በጥርሱ አላመጠ፣ ትኩሳቱ የፈጠረለት ህመም፣ ከንፈሩ ላይ አሻራ ስሏል፡፡ የሆነ ስስ ላስቲክ የመሰለ ቆዳ በጥርሱ እንደክር መዘዘ፡፡ ህመም ተሰማው፡፡ ልቡ በስሱ ልቧን ታንኳኳለች ”ማነው…” የሚላት ባታገኝም፡፡ አናቱ ላይ ክምብል ሊል የደረሰ በሚመስለው ጣሪያ በኩል ዝናቡ እኝኝ የሚል ለዛቢስ ዲስኩር ይደሰኩራል፡፡ ጣሪያው ማሳበቁ ይገርማል፡፡
እነዚህን ሁሉ የድብርት ጥርቅም በአለባበሱ ለመደለል ያደረገው ጥረት፣ ከግማሽ በላይ ሚዛን ደፍቶለታል፡፡ ልክ ህዝቦቿ በርሃብ ኩል ጠልሽተው፣ በሆነ አሀዝ እድገታችን ከፍ ብሏል ብላ እንደምታቅራራ ሃገር ተሽሞንሙኗል፡፡
እንየው…በመኮሳተር መስመር ውስጥ ተጨማዶ ፊቱን ደጋግሞ ተመለከተው፤ የገዛ ፊቱን ተጠራጠረው…የሌላ አስቀያሚ ሰው ፊት አምጥተው የለጠፉበት ይመስል…በዛ በከሰለው መልኩ ድራቢ…ውዳሴ እየሳቀች ተመለከተ፡፡ ሳቋ…ማህሌታይ ያሬድ የፈጠረውን “ኖታ” ተመርኩዞ የሚዘምር አይነት ነበር፡፡
የመስኮቱን መስተዋት ላለማየት መጋረጃውን በእልህ ደረገመው፡፡
ሮጦ መኝታ ቤት ገባ፡፡
ተመልሶ ለመውጣት ቃጣ…
እያደረገ ያለው ድርጊት ተቆጪ እንዳጣ ሞልቃቃ ህፃን መንቧቸት ሆነበት፡፡
(ቁንጮዎቻችን እንኳ እንደፈለጉ ሲሆኑ “ለምን?!” ማን ብሎ ያውቃል፡፡)
የውዳሴ መኳኳያ መስተዋት ከአልጋው በስተቀኝ በኩል በቁመቱ ዠቅ ብሎ እንደ መልከመልካም ልጃገረድ አምሮ ተሰይሟል፡፡ አሁን ሙሉ እሱነቱን በደንብ አተኩሮ ተመለከተው፡፡ ህሊና ሲበረበር ይሄንን ይመስላል፡፡ በቀፈፈው ስሜት ፊቱን ሲመለከተው፣ የጠፋ አመድ ላይ የተንከባለለ ሙሽራ መስሏል፡፡ የለበሰው ሙሉ ልብስ ግን “ሰው” የሚለውን ስም ለጥፎለታል፡፡
“እመቤት ለምን ዛሬ ቀጠረችህ?” መስተዋቱ ውስጥ ያለውን እንየው ጠየቀው፡፡
በቀለም ያበደውን ፀጉሯን እየቆነጠረች፣ በሳቅ ቀምማ የትምህርት ቤት ፍቅራቸውን ከትረካ ማህደሯ መዝዛ ስትተርክለት፣ ብብቱን እንደተኮረኮረ ህፃን እሚጥም ሳቅ እየረጨ ሰማት፡፡ ስስ ብልቱ እንደተነካ ተመጽዋች ፍቅረኛ ፍርክርክር አለላት፡፡ ቀድሞም ስለምታውቀው ሳያስበው መዳፏ ውስጥ ያስዋኘላትን አጋጣሚ የማምለክ ያህል ተንበረከከችለት፡፡ ሴት ልጅ የመረቧ ውል ጠፍቶባት አያውቅም፣ አውቃ ካልረሳችው በቀር፡፡
መስተዋቱ ውስጥ…ውዳሴ እና እመቤት አጠገብ ላጠገብ ሆነው…ውዳሴ በንጽህና እንደተሰጠ የቤተክርስቲያን እጣን ቀጥ ብላ ስትጐን…መዓዛዋ ደረሰው፤ ነፍሱ ውስጥ የሸሸገውን እውነት አወደበት፡፡
እመቤት ግን ሳቋ ንፍሮ እንደሚቀቅል ውሃ ወይቦ ሲንተከተክ ታየው… ከጀርባቸው… ያ… ተሸናፊው እንየው፤ ጥሬ ትዝብቱን እየቆረጠመ የሚሆነውን በአግራሞት ኩል እየኳለ ተገትሯል፡፡ አንድ የሆነ ሁለትነት…በአንድ ግማሽነት የጅል አድራጐት ግራ መስመር ላይ እየተጠጋ አፋፉ ጋ ነው፡፡ (መሪም ግራ ሲገባው የህዝቡን ጣት ይጠባል!)
የእመቤት ሳቅ የጆሮውን እምብርት ሲደቃው አመመው፡፡
ከውዳሴ ጋር በማይረባ ነገር ተኳርፈው ከቤት ሲወጣ…ጭር ያለው ጐዳና ላይ ያለ ገላጋይ በመኪናዋ እየፈሰሰች…እሱም እሷም ባላሰቡበት ሁኔታ፣ የጊዜ አቃጣሪ ቀሽም ብልሃት መዞ፣ እንየው ስም እንደበዛበት ጧፍ እየነደደ እያለ ተያዩ…የመኪናዋን የድምጽ ርችት ሊንቀው ጉልበት አልነበረውም፡፡
“ብረትን መቀጥቀጥ እንዳጋለ ነው” ፍቃዱን ሳትጠይቅ ተንጠራርታ፣ ወዝ የጠገበ አብረቅራቂ መቋሚያ የመሰለውን እጇን ልካ በሩን ከፈተችለት፡፡ ገባ፡፡ ቀጥታ ለሠላምታ ጉንጯን አሞግጋ ላከችው - ከትኩስ ፈገግታ ጋር፡፡
እንየው፤ ከውዳሴ ጋር የተጋጨበትን ቀጭን ቅሽምና አምሮ ጠላው፡፡ አይወጣም ነበራ ከቤቱ…አያገኛትም ነበራ እመቤትን፡፡ ከስንት ዓመት በኋላ…
ሲሳሳሙ የከንፈሯ ወላፈን የከንፈሩን ጠርዝ በስሱ ገረፈው፡፡ ትዝታ ለመርጨት ነበር ስልቷ፤ ደግሞ እመቤት መሳም እንደተካነችበት አሳምሮ ያውቃል…እሷም ልሳም ብላ ከሳመች አቅልጤ መሆኗን አሳምራ ታውቃለች፡፡ ልቡ ነዳጅ መስጫው እግሯ ስር ሲወድቅ ታወቀው…ትረግጠው ይሆን…?
አይኑን ያገኛቸው፣ ዝገኑኝ ይመስል ከልብሷ አፈንግጠው ከወጡት ጡቶቿ ላይ ነው፡፡ “ተበልተሃል” ስትል በልቧ ያዜመችውን ልቡ ነገረው፡፡ የሆነው ሁሉ ሆነና…እማይሄድበት ቦታ ሸኝታው…የዛሬ ቀጠሮው ላይ ጥዳው ተለያዩ፡፡ ዘይቱ የጐደለበት ቀንዲል መስሎ በርቷል፤ ጭልጭል እያለ የኋላው ትዝታ፡፡
አሁንም ምስልና ሳቋ መስተዋቱ ውስጥ እየታየው ነው፡፡
ውዳሴ…ከደርባባ ፈገግታዋ ጋር የመልካምነት ነጠላ እንደለበሰች ከቅዳሴ እንደተመለሰች ሴት አምራ ታየችው…ከፊቱ በላቀ…አማረችው፣ አሳሳችው፣ ለመቅለጥ ጥግ ላይ ሆኖ አየው ራሱን፡፡ የትኛው ነው ዋናው እንየው…?
እዚህ በቆመበት የቆመው ወይስ ከእነዛ ሁለት ሴቶች ጀርባ የቆመው…?
(የብዙሃኖች ሃገርስ የቷ ናት…? አንገታቸውን የሰበሩት የሚኖሩባት ወይስ… ጥርሳቸውን እየሟጩ የሚያፋጩ… እሚፏልሉባት!)
በሁለት ነኝ ባይ አንድነት ውስጥ የጣሉትን አንስቶ የያዙትን መጣል ለማን ይበጃል…ውኃ የተሞላ የባሎን ላስቲክ እንደምን አየሩ ላይ ደረቱን ሰጥቶ መተኛት ይቻለዋል…? እንየው፤ ምርጫ የሌለው ምርጫ ውስጥ ተሸሽጓል፡፡ ትላንትናው በልጦ ዛሬውን ሊነጥቀው እየተሳለቀበት ፊት ለፊቱ ተገትሯል፡፡ እውነት ደግሞ ብርታቱ ከገዛ ልብ ሃገር ያሰድዳል፡፡
ውዳሴ…አኩርፋ ብትስቅ እንኳ የሳቋ እቅፍ ያሞቀዋል፤ ራቁት ነው ልቧ፡፡ ለሰከንድ እንየውን ተጠራጥራው አታውቅም፡፡ አንዲት የእሳት ፍንጣሪ አይኗ ውስጥ ዘልቃ አታውቅም፡፡ ለፍቅር ተፈጥራ አፍቅራ ማለፍ የምትችል ነጭ ላባ የሆነች ሴት ናት፡፡ ህዝቦቹን እንደሚፈራ መሪ እየባተተች አትኖርም፡፡ በህዝቦቿ እንባ ገላዋን እንደምትጐስም ሀገር ግን ፍቅር ተርባም ታምራለች፡፡
እመቤት…በሳቋ ኩርኩም የወንድን ልጅ የልብ ስስ ብልት እምታደማ፣ እንደጭቅና ሥጋ ስስ ማንነት የያዘች “ሲሆን ይሆናል ካልሆነ ምናባቱ”ን የተቃኘች ናት፡፡ ጠዋት በማመን እንቅፋት የፍቅሯ ጣት እንደቆሰለ እስካሁን አልዳነላትም፡፡ ያጣችውን ለመስረቅ፣ ለማካካስ የምትሮጥ አይደርሴ ሯጭ ሆናለች፡፡ እንየው፤ እቺን ያልተገረዘች ሴት አያውቃትም፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ የከንፈርም የአልጋም በረከት የተሸለመው፣ ድንግልና ወስዶ ያስወሰደውም ከእመቤት ነው፡፡ ያኔ በሽንገላ ሳቅ የታሸች ጨጨብሳ አልነበረችም፤ ጣፋጭ ጭኮ እንጂ፡፡ ስሟ ሲጠራ እና ሲያያት ውኃ ውስጥ እንደከረመ ተልባ ይማልጋል፣ ውኃው ሲናጥ ደግሞ አረፋው ተኩረፍርፎ ይቀራል፡፡
በመስተዋቱ ውስጥ ሶስቱንም ተመለከታቸው…ወንዱን ግን ጠልቶታል…እነቀው እነቀው የሚል ስሜት ተሰምቶታል! እንዴት ሰው በራሱ እግር መቆም ያቅተዋል…! ለዚህ ነው ወደ ውስጥ በተመለከትን መጠን ለራሳችን ያለን ግምት ሚዛን ላይ የሚወጣው… ራሱን ከራሱ ጋር ያልመዘነ “ሰውነት” ደግሞ አስጊ ነው!
ውዳሴ…አምሮባት…መታመን ግንባሯ ላይ ታትሞ…ቁንጅናዋ የለበሰችው ነጠላ ላይ ፈገግ ብሎ ተመለከተ፡፡ እምነት ለፈጣሪ የሚሰጥ የሰባ መስዋዕት ነው፡፡ (መታመን!) ውዳሴ ከሳቀች ደግሞ ቋንጣ ታቀልጣለች፡፡ እመቤትማ ሳቋ ለጠላት እንደተተኮሰ (ለወዳጅ ይተኮሳል እንዴ?) መትረየስ ሲንጣጣ…ጠመዳት!
ሙሉውን የመስተዋቱን ስፍራ ተንደላቀቀችበት…ልክ ለሀገሪቱ እናውቅላታለን እንደሚሉት አይነት፡፡ “እቺን ሴት አላውቃትም እንዴ”…? አለ ለራሱ፡፡
ከውዳሴ ጋር በምን ተዐምር ይመጣጠናሉ…የትኛውስ ሚዛን ነው ልኩን እሚያውቅ!፡፡
“ለምንድነው እንገናኝ ብትይኝ እሺ ያልኩሽ…?” አምባርቆ ጠየቃት፡፡
“ትወደኛለህ…አውቃለሁ…” የአመላለሷ ልስላሴ ከሃር ያይላል…ያንን እሚያመውን ሳቋን ሳቀችበት…የመድፍ ያህል ለቀቀችበት፡፡
“በእናትሽ ይሄ ልብ የሚገሸልጥ ሳቅሽን አቁሚና…ምን አስበሽ እንገናኝ አልሺኝ…?” መስተዋቱ ላይ አፈጠጠ…በቀኝ እጁ ግራ ጣቱ ላይ ያጠለቀውን የክብር ቀለበት እያሽከረከረ ነበር፡፡ ይሄ ሰው ሞኝ ነው እንዴ…
“ፍቅር እኮ የጥጥ ፍራሽ ነው መታደስ አለበት…” ቀስ ብላ ለጆሮው መጥና ነገረችው፡፡ ሳያስበው ከጣሪያ ስር ሳቀ…እንዲህ ስቆ አያውቅም፡፡
“እንሽዬ፤ ለእኔም የመጀመሪያዬ ላንተም የመጀመሪያህ ነኝ” ቀለበቷ እንዲታይላት ነው መሰል አፍንጫዋ ላይ ምንም ሳይኖር አበሰችው፡፡
“አውቃለሁ…” ደደብነሽ ይመስላል አመላለሱ፡፡
“እንደምታውቅ ይገባኛል…!” ወደፊት ተጠጋችው…ፍሬሙ ጠበባት መሰለኝ ለመውጣት ተቸገረች… “ምነው ፈራህ?” ሲያፈገፍግ አይታው ስታፈጥበት ተገርሞ ግምባሩን ቅጭም አድርጐ ተመለከታት…ራሷ ናት…ከንፈሮቿን ያውቃቸዋል፡፡ ለወራት ዋኝቶበታል…ዐይኖቿም የራሷው ናቸው…ጡቶቿ ግን በውበት ብዛት ልክ እንዳጣ ስዕል ሆኑበት፡፡ ውብ ናቸው ግን ለቴስታ የተመቻቸ ኳስ መሰሉት…ፈራት… የዛችን ሃገር ህዝቦች ማንም ታግያለሁ ባይ ከመሬት እየተነሳ እንደሚያስፈራራው አይነት ተሸማቀቀ…
“ለምን…? ትዳር እንዳለኝ እያወቅሽ ድክመቴን ተጠቅመሽ ትጥይኛለሽ…? በደካማ ጐኑ ሰውን መጣል ደግሞ ደፋር አያሰኝም…”
“ቆይ ተረጋጋ ምን ተፈጠረ…ለምን ሃገሩን እንደተቀማ ሽፍታ ትንጨረጨራለህ…”
“ያው ነው! ያው ነው!...ሚስትም ሃገር ናት፤ ሀገርም ሚስት ናት!...”
“ተሳስተሃል…ሃገር ሚስት ሳትሆን እናት ናት…ሚስትማ ብትሆን ይሄ ሁሉ ሞልፋጣ ስንት ራስ ወዳድ ያስቀፈቅፋት ነበር…”
“ወዴት ወዴት…ምንድነው ምትዘባርቂው!”
ያን ቀለሙ የተዘበራረቀውን ሳቋን ሰጠችው፡፡ እየተወራጨ አይኑን ጨፍኖ፣ ጆሮዎቹን በሁለት እጆቹ ግጥም ጭምቅ አድርጐ ይዞ፣ ለጥቂት ደቂቃ አጐንብሶ ቀረ፡፡
የውዳሴ እጆች እየዳበሱ ካጐነበሰበት ቀና ያደረጉት መሰለው…
ራሱን ቀጥ ብሎ መስታወቱ ፊት ለፊት አገኘው…እመቤት የለችም፡፡ ያኛው እንየው እና ውዳሴ አጠገብ ላጠገብ ቆመዋል፡፡ ያኛው እንየው የተረበሸና የተቃጠለው ገጹ የተወለወለ ባዶ የፎቶ ማስቀመጫ “ፍሬም” መስሏል፡፡ አጠገቡ ውዳሴ በመኖሯ የሆነ አበቦች መሃል የበቀለ ለአይን አያስጠሌ ነገር መስሏል፡፡
ዋናው እንየው… ልብሱን ማስተካከል ያዘ፡፡
ቀጥ ብሎ ቆመ፡፡
ብቻውን ነው፡፡
መስተዋቱ ውስጥም ከመስተዋቱ ሌላ ማንም የለም፡፡
ሰው ራሱን ከሆነ… ራሱን ብቻ ነው እሚመስለው!
ያልቆረጠው ልቡ የተቆረጠለትን ቀጠሮ እንደ ደጀሰላም ደወል ደወለለት፡፡ ከረባቱን አጠለቀ፡፡ ጥቁር ጣልጣል ያለበትን ቀይ መደብ ከረባቱን ዳበሰ፡፡ ግራ ደረት ኪሱ ውስጥ የተቀመጠችውን ቀይ መሃረብ እስካሁን አላያትም፡፡ ማነው ያስቀመጠው…? ማስታወስ አልቻለም፤ ግን ግን… የሆነ ቀን ይሄን ከረባት ውዳሴ ቦርሳዋ ውስጥ ስትከተው አይቷል፡፡ ላውንደሪ ልትሰጥለት ነው የመሰለው፡፡
መሀረቧን መዞ ሲያወጣት አንዳች መአዛ መንፈሱን አወደው… ለመጀመሪያ ቀን ውዳሴን አንገቷ ስር ሲስማት የሸተተው ሽቶ… ከገነት አበቦች ተቀምሞ የተሰራ ሽቶ… እድሜ ዘላለሙን ከህሊናው ጐታ የማይወጣ!
ጩህ! ጩህ! አሰኘው… አናወዘው… ዝቅ ሲል… የተጣጠፈች ወረቀት እግሩ ስር ለይቅርታ እንደተንበረከከ በዳይ ተንበርክካለች፤ ቀና ሲል ያኛው እንየው መስተዋቱ ውስጥ አፍጦ ቆሟል… ሳቀበትና “አንሳው እንጂ!” አለው፡፡
አሁን ይሄን ሰው ያምነዋል…
ዝቅ አለ፡፡
በዝቅታ ውስጥ ያለ ከፍታ ልዩ ስፍራ አለው፡፡
ይቅርታሽን ተቀብያለሁ ይመስል ወረቀቷን በሁለት እጁ ድምቡሽቡሽ ህፃን እንደሚስም አይነት በፍቅር አነሳት… ባለቀለም ወረቀት… አስተጣጠፏ በስርአት የተተኮሰ ሸሚዝ ይመስላል፡፡ ቀስ ብሎ ገለጠ… ምስሏ ከሩቅ… ከሰማየ ሰማያት የምትታይ የምትመስል የዋህና ታማኝ ሴት… ፈገግታዋን ቆጥባ የፈገገች ሴት ምስል ከፊደሎቹ ትከሻ ላይ ታየው፤ ፊደሎቹን ስለሚያውቃቸው ነው ምስሉ ቀድሞ የመጣለት… አጣጣሎቹ እንደ ውዳሴ የሳቁ ናቸው፡፡
“ውዴ” የሚለውን የተሰበረን የሚጠግን ቃል… ጐላ አድርጋ የምትፅፈው እሷ ናት፡፡ የተከረከመ የፅድ አጥር የመሰለው የእጅ ፅሁፍ ላይ አፈጠጠ…!
ሲጀምር… “ውዴ…” ይላል…
“ለምን ስትል ይከፋሃል… እኔ ሁልጊዜ አጥፊህ ነኝ… አንተ ደግሞ በይቅርታህ ላጲስ ስህተቴን ታፀዳልኛለህ… አውቃለሁ… ትወደኛለህ… አውቃለሁ እወድሃለሁ፤ እናውቃለን እንፋቀራለን… ስለምን ትከፋብኛለህ…? አንተን ከፍቶህ ከማይ… ለምን ቀኔን አይቀሙኝም! ያን ስላንተ እመርጣለሁ፡፡
ውዴ፡-
ስወድህ እኮ መጠንና ልክ የለውም… በወደድኩህ መጠን ሰፍሬ ሳስበው መልሼ እጥፉን እወድሃለሁ፡፡ መለኪያው ምንም ነው፡፡ ይሄ ነው አይባልም መጠኑ… ስትስቅልኝ እስቃለሁ… ሲከፋህ ግን ጨረቃ እግሬ ስር ተንበርክካ ብትለምነኝ እንኳ አልስቅም፡፡ ደስታ ከኔ ትርቃለች፡፡ አንተን ሲከፋህ እምነጠቀው ነገር ይበዛል፡፡ እየሆንኩ ያለውን ሳስበው… እማልሆንልህ እንደሌለ፣ ይበልጥና ላንተ ስል መራራውን ለማጣፈጥ እጥራለሁ፡፡ ደግሞ አብረኸኝ ካለህ ምንም ነገር ሊመረኝ አይችልም፡፡ ጣፍጠህ ታጣፍጠኛለህ፡፡
ውዴ፡-
አውቃለሁ… አስደስቼህ አላውቅም… አንተኮ ነህ የቀን ተቀን አረሜን ነቅለህ፣ እንክርዳድ አልባ መልካም ፍሬ ምታደርገኝ፡፡
አንተ’ኮነህ… አሸዋ ላይ ተተክዬ እምለመልም አበባ ምታደርገኝ…
አንተ’ኮነህ… ሳቄን እንደሚጣፍጥ ሙዚቃ እምትቀምምልኝ…
አንተ’ኮነህ… መኖሬን እንደውብ ግጥም በዜማ አሳምረህ ምጣኔውን አስተካክለህ… ስልት ባለው ክራር አጅበህ… ለነፍስ ጆሮ እንዲመጥን አድርገህ ምታነበኝ…
አንተ’ኮነህ… መውደቄን ወድቀህ ምታቆመኝ…
አንተ’ኮነህ… እንባዬን አብሰህ አይኖቼን ስመህ “እዪ” ምትለኝ…
አውቃለሁ… ታውቃለህ እንደምንፈቃቀር…፤ ስለምን ያ ሁሉ ጉልበትህ ዝሎ ትከፋብኛለህ…? ስትወደኝ መጠንና ልክ የለውም፡፡ በወደድከኝ መጠን ሰፍረህ ስታስበው መልሰህ እጥፉን ትወደኛለህ፡፡
አውቃለሁ፡፡
መለኪያህ ይቅርታ ነው፡፡
ስህተቴን በይቅርታህ መደምሰሻ አሻራው ሳይገኝ እንደምትደመስስልኝ…
ስለማውቅህ… አውቃለሁ፡፡
ውዴ…
ስለምን ሰዎች በፍቅር መኖር እየቻሉ በቁጣ ስለት አብሮ የመኖርን ገላ ቀርድደው ይጥላሉ…? ስለምን አንዱ ያንዱን ጉድፍ አያብስም…? የራሱ እንዳለ ሆኖ!
ስለምን እኔ ላንተ አንተ ስለእኔ አንኗኗርም… ሁለት የሆነ አንድነትን ስለምን በአጉል ሌላ መሻት እንደ ሰበዝ እንሰነጥቀዋለን… ስለምን…? ቀለም ያለን… አለላዋች መሆን አቃተን…፤
ውዴ፡-
እኔ አይደለሁ ደምቄ፣ አምሬ፣ እየታየሁ ህሊናህን በቅናት ጅራፍ ምገርፍህ… እመነኝ ካንተ ውጪ ለማንም አምሬ አልታይም፣ ቀድሞውኑም አንተኮ ነህ ማማሬና ውበቴ፡፡
ውዴ፡-
አንተ’ኮ ለእኔ ቤተክርስቲያን እንደሚሰጥ ከንፁህ ማሳ በቅለህ የተገኘህ ዘቢብ ነህ… “በቃሽ” ወረቀቱን ደረቱ ላይ አጣብቆ ውዳሴን ያቀፈ እስኪመስለው ተጠመጠመበት፡፡ “ለምን እናት…? ለምን…? የእኔን ቅጥ ያጣ ሃጢያት አንቺ ትሰሚያለሽ… ያንቺ ፍቅር እኮ እንደ ሞት የበረታች ናት… የእኔ ቅናት ግን እንደ ሲኦል የጨከነች ናት…! እኔ’ኮ ነኝ በዳይሽ… እኔ ነኝ ስቃይሽ… እኔ ነኝ ካስቀመጥሽኝ ቦታ በመንፈስ ተንሸራትቼ የወደቅሁት… አንቺ ምን አደረግሽ…?”
እንደረታችው ገባው… አንተ ነህ ጥፋተኛ ሳትል ፍቅሯን ፅፋ ሰጠችው… ስህተቱን መዞ አወጣ፡፡ ደብዳቤዋን ሳመው… እቅፍ አድርጐ ተንበረከከ… ደጋግሞ ደጋግሞ “ለምን…! ለምን…! ለምን…!” እያለ ጮኸ… ዘቢብነቷ ጣመው… ናፈቀችው… ስርዝ ድልዝ የበዛበትን ልቡን በንፅህናዋ አረመችው፡፡ እሷ ዘቢብ ነበረች… እንዳልበሰለ ኮሽም የሚኮመጥጥ ስሜቱን ያጣፈጠችለት… ባዶ እግሩን የደቀቀ ጠርሙስ ስባሪ ላይ ሲራመድ ተነጥፋ እሷን ተራምዶ ነው የቆመበት ቦታ ላይ የቆመው፡፡ እሷ ስለሆነች ነው አሁን የሆነውን የሆነው፡፡ አጥፍቶ ልሂድ ባይን “መንገዱን ጨርቅ ያድርግልህ” ሳይሆን፣ ተበዳይ በዳይ መስሎ ይቅርታ ሲጠይቅ፣ አስረዝመው ያሰሩትን በእምነት ይፈቱታል፡፡ ሐገርም እንዲያ ናት… እንደ ልባም ሴት… “ስለምን” እያለች እምትለምን፡፡ ስለ አንድ ልጇ መውደቅ እምትሰበር፣ በእንባዋ መሃል ሳቅ እምትፈትል… “ውዴ” እያለች ልጆቿን እምትጠራ…
እንየው፤ በሁለት እጁ ግጥም አድርጐ የያዘውን ደብዳቤ ተመለከተ… በእንባው በስብሷል… ታሪክ ነበር… ይብዛም ይነስ እያንዳንዱ ሰውና ሃገር ታሪክ አለው፡፡ ፊደሎች ጠቀሱት… ፈገገ፡፡ የምርም ይቅርታ ነበረባቸው፡፡ የምርም ሰው መሆን ነበረባቸው፡፡ የምርም ያዘመመ ጐጆን ቀጥ አድርገው የያዙ ባላዎች ነበሩ፡፡
ከአይኑ አቆማዳ የሚንጠባጠቡት እምባዎች መዳፉ ላይና ከበሰበሰው ደብዳቤ ላይ ባዶ ስፍራ መርጠው የሆነ ነገር እየፃፉ አያቸው…
መዳፉ ላይ፡-
“የጠቢባን ልብ በለቅሶ ቤት ነው፡፡ የሰነፎች ልብ ግን…በደስታ ቤት ነው፡፡ ሰው የሰነፎችን ዜማ ከሚሰማ ይልቅ የጠቢባንን ተግሳፅ መስማት ይሻለዋል፡፡ በሰነፎች መካከል ከሚጮህ ከገዢው ጩኸት ይልቅ የጠቢባን ቃል በፀጥታ ትሰማለች፡፡ ከጦር መሳሪያዎች ይልቅ ጥበብ ትሻላለች… አንድ ኃጢያተኛ ግን ብዙ መልካምን ያጠፋል…” ይላል፡፡
ደብዳቤው ጐን ላይ ደግሞ፡-
“የእግዚአብሔር መስዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፡፡ የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ እግዚአብሔር አይንቅም፡፡”
***
“ሰው በልቡ አምኖ ይፀድቃልና… በአፉም መስክሮ ይድናልና…”
በሩ ተንኳኳ…
አይኖቹን በእንባ እንደ ኳለ… በሩ ላይ ወረወራቸው…
“ግቡ…”…
የልቡ በር ተከፈተ…፡፡

Published in ልብ-ወለድ

እንኳንም ኦክስጂን በኤሌክትሪክ የሚሰራ አልሆነ --- (አበሻ አልቆለት ነበር!)
የመብራት መቆራረጥ በክረምት ተሳበበ (climate change አይሻልም ?)

ባለፈው ሳምንት አርብ ምሳ ሰዓት ላይ ነው፡፡ ቁጭ ብዬ የኢቴቪን ዜና እየኮመኮምኩ ነበር፡፡ ዓይኔ ቲቪው ላይ ተተክሎ ቀልቤ ግን በሌላ የግሌ ሃሳብ ተወስዶ ኖሮ ድንገት ወደ ጆሮዬ ዘሎ የገባው ትኩስ የሙስና ወሬ ቲቪውን በሙሉ ልብ እንድከታተል አነቃኝ፡፡ “የኢትዮጵያ መብራት ኃይል ኮርፖሬሽን ዘጠኝ ሃላፊዎች በ450ሚ. ብር ሙስና ተጠርጥረው ተያዙ” ይላል የኢቴቪው ዜና፡፡ ወዲያው ምን አልኩ መሰላችሁ? “ሙስና በየተራ!” ይሄን ያልኩት ግን ለሰው አይደለም ፤ ለራሴ ነው (አጠገቤ ማንም አልነበረማ !) እኔ የምለው ግን--- ይሄ እየተባባሰ የመጣው የመብራት ብልጭ ድርግም (የገና መብራት መሰለ እኮ!) የሙስናው ውጤት ይሆን እንዴ? መሠረተ ቢስ አሉባልታ የሚባለው ዓይነት እንዳይመስላችሁ፡፡ የሰማሁትን ሰምቼ እኮ ነው፡፡ የኮርፖሬሽኑ ሃላፊዎች ከተጠረጠሩባቸው ወንጀሎች አንዱ ---- አዲስ ትራንስፎርመሮች እንዲገዙ ቢታቀድም ትራንስፎርመሮቹ ተገዝተው ሲመጡ “አሮጌ ሆነው ተገኙ” ተብሏል፡፡ እንደኔ የዋህ ከሆናችሁ “ትራንስፎርመሩ የተገዛው ከህንድ ስለሆነ በአስማት አጭበርብረዋቸው ይሆን እንዴ?” ልትሉ ትችላላችሁ፡፡ ግን እድሜ ለፀረ- ሙስና ኮሚሽን! ነገርየው ምንም አስማት እንደሌለበት ታውቋል፡፡ (ሙስና ራሱ እኮ የለየለት አስማት ነው!) 

አይገርማችሁም ግን ---- ከፊሉ አባይን ለመገደብ መከራውን ሲበላ፣ ከፊሉ “ሆዱን ለመገደብ” ይሯሯጣል፡፡ ይሄ ባለፈው ጊዜ ኢህአዴግንና ተቃዋሚዎችን “ሲያባላቸው” የነበረው ኮንሰንሰስ (ብሄራዊ መግባባት) የሚሉት ነገር እንደገና መመርመር ያለበት መሰለኝ፡፡ ወይም የቃሉ ትርጉም በይፋ ይቀየር፡፡ (በቃሉ ላይም ኮንሰንሰስ ያስፈልጋል !) እውነቴን እኮ ነው---- እንኳንስ ኢህአዴግና ተቃዋሚዎች ቀርቶ ራሳቸው ኢህአዴጎች መች ኮንሰንሰስ ላይ ደረሱ? እንዴ---- አንዱ እያለመ ሌላው እያወደመ “ብሔራዊ መግባባት” አለ ይባላል እንዴ? ከፊሉ ኢህአዴግ ልማታዊ፣ ከፊሉ የልማታዊነትን ካባ የደረበ ኪራይ ሰብሳቢ፣ የቀረው ደግሞ ዓይኑን በጨው የታጠበ ኪራይ ሰብሳቢ በሆነበት አገር ምን ዓይነት “ኮንሰንሰስ” ነው አለ የሚባለው? እንግዲህ ራሱ ኢህአዴግ የሾማቸው የራሱ አባላት ናቸው የሙስና አረንቋ ውስጥ ገብተው እየዳከሩ ያሉት? ይቅርታ አድርጉልኝና --- እንደውም እኮ “ኮንሰንሰስ” የተፈጠረ የሚመስለው በሌላ ላይ ሳይሆን በሙስና ላይ ነው፡፡ (ሁሉም ተዘፈቀበት እኮ!)
እኔ የምለው --- ለመሆኑ የመብራት ነገር እንዴት እያደረጋችሁ ነው? ሰሞኑን ለኢቴቪ ምሬታቸውን የገለፁ የመዲናዋ ነዋሪዎች፤ የመብራት መቋረጥ በሥራቸው ላይ ትልቅ እንቅፋት እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡

(ፀረ-ልማት ማለት ይሄው አይደል!) አንድ ወይዘሮ እንደውም ሥራ ብቻ ሳይሆን እህልም ከልክሎናል ብለዋል - አብስለው መብላት እንኳን መቸገራቸውን በመጥቀስ፡፡ ወይዘሮዋ አክለውም ሊጋግሩት ያዘጋጁት ሊጥ በመብራት መጥፋት ሳቢያ፣ እየተበላሸ ለመድፋት መገደዳቸውን በምሬት ተናግረዋል፡፡ ሌላዋ ወይዘሮ ደግሞ መብራት ከጠፋ በኋላ ድንገት የሚለቀቀው ከፍተኛ ኃይል ንብረቶቻቸውን እያቃጠለባቸው መሆኑን ገልፀው “እቃ እቃ እየተጫወቱ ነው” ሲሉ መብራት ኃይልን ወቅሰዋል፡፡ (አቃጥሎ ቢከፍል ደሞ የአባት ነው!) ምን ይሄ ብቻ--- የመብራት ኃይል ጦስ በቴሌኮምና በውሃና ፍሳሽ ሳይወሰን ለኢቴቪ መትረፉን ሰሞኑን ራሱ ኢቴቪ ዘግቧል፡፡ በወሎና አካባቢዋ ፣ ነዋሪዎች የሬዲዮና ቴሌቪዥን ሥርጭት እንደተቋረጠባቸው የገለፁ ሲሆን የመቋረጡ መንስኤም የመብራት መቋረጥ መሆኑ ተጠቁሟል (ሬዲዮም አላሰማ፣ ቴሌቪዥንም አላሳይም እኮ ነው!)
እየተባባሰ መጥቷል ስለተባለው የመብራት መቆራረጥ ችግር የተጠየቁት የኮርፖሬሽኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ፣ ከወትሮው የተለየ አዲስ ሰበብ ፈጥረዋል (በፈጠራ ክህሎታቸው ተደምሜአለሁ!) አዲሱ ሰበብ ምን መሰላችሁ? የክረምቱ የአየር ንብረት ነው! (እንኳንም climate change ነው አላሉ) ሃላፊው እንደሚሉት፣ ነፋስ የቀላቀለ ሃይለኛ ዝናብ የኃይል መቋረጥ እያስከተለ ነው፡፡ ምን እንደጠረጠርኩ ታውቃላችሁ? የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው፣ በበጋ ወቅት አገር ውስጥ የነበሩ አልመሰለኝም (“በዚያ በበጋ በዚያ በክረምት--እጮኛ ጠፍቶ በፍለጋ--” የሚለው የልጅነት መዝሙር ትዝ አላችሁ?) እዚህ ቢኖሩማ ---- ዓመቱን ሙሉ ክረምት ከበጋ ሳይል በመብራት መጥፋት ምን ያህል መከራችንን እንደበላን ያውቁልን ነበር፡፡ (መግለጫ ከመስጠታቸው በፊት መረጃ ቢጠይቁ ሸጋ ነበር!) በእርግጥ ለኃይል መቆራረጡ ሌሎችንም ምክንያቶች ጠቅሰዋል - የኃይል ማሰራጫና ማከፋፈያ የጥራት ችግሮችን፡፡ (9 የኮርፖሬሽኑ ሃላፊዎች በሙስና መጠርጠራቸውን ያዙልኝ!) እኔ የምለው ግን----አንድ ነገር ከአቅም በላይ ሲሆን “አልቻልኩም--- አቅቶኛል!” ማለት ነውር ሆነ እንዴ? (ቢሆን ነው እንጂ!) ያለዚያማ የኮርፖሬሽኑ ዋና ዋና ኃላፊዎች፣ እስካሁን ለሚችል አስረክበው ወደሚችሉት ሥራ ይገቡ ነበር፡፡ (ኦክስጂን በኤሌክትሪክ የሚሰራ ቢሆን ኖሮ አበሻ በአየር እጦት አልቆ ነበር!)
ሰሞኑን ሰምቼው በአግራሞት የሞላኝ ዜና ምን ይላል መሰላችሁ? “በመንግስትና በፓርቲው (ኢህአዴግ ለማለት ነው) መካከል ጥብቅ ትስስር ለመፍጠር ታቅዷል” እንዴ--- ኢህአዴግና መንግስት ከዚህ በላይ ምን ዓይነት ጥብቅ ትስስር ሊፈጥሩ ነው? “ኢህአዴግ ማለት መንግስት፣ መንግስትም ማለት እኮ ኢህአዴግ ነው” እንግዲህ አዲሱን ዓይነት ትስስር ደግሞ እድሜና ጤና ይስጠንና አብረን እናየዋለን፡፡ ሌላም አስገራሚ ዜና ሰምቼአለሁ - በዚሁ ሳምንት፡፡ አንድነት ፓርቲ በሰጠው መግለጫ መሰረት፣ የፀረ- ሽብር ህጉን በሰላማዊ ትግል ለማሰረዝ የአንድ ሚሊዮን ሰዎችን ፊርማ የማሰባሰብ ዘመቻ መጀመሩን በይፋ የገለፀው ፓርቲው፤ ሰሞኑን በዚሁ እንቅስቃሴ ላይ የነበሩ 42 አባላቱ ፈቃድ የላችሁም በሚል ተይዘው ከታሰሩ በኋላ በዋስ መለቀቃቸውን በመጠቆም “ለተፈፀመብን ህገወጥ ተግባር የሚመለከተውን አካል እንከሳለን” ብሏል፡፡ (የህግ የበላይነት የሚከበርባት አገር ስለሆነች መብቱ ነው!) አንድነት ፓርቲ የተፈፀመብን ህገወጥ ተግባር ነው ይበል እንጂ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ፤ “ከቤት ውጭ የሚደረግ ማንኛውም ቅስቀሳ ፈቃድ ያስፈልገዋል፤ ካለፈቃድ የሚደረግ እንቅስቃሴ ህገወጥ ነው” ብሏል፡፡
እኔ የምለው--- ፓርቲው ህጋዊ አይደለም እንዴ? (ለጠቅላላ እውቀት ነው!) ለማንኛውም ግን ህገወጥ ነው የተባለው የእንቅስቃሴ ዓይነት በግልፅ ቢታወቅ ጥሩ ይመስለኛል (በእውቀት እጥረት መታሰር ደስ አይልማ !) አሁን ለምሳሌ ሩጫም እንቅስቃሴ ነው (በታላቁ ሩጫ የታሰሩ እንደነበሩ ልብ ይሏል) ወደ ት/ቤት መሄድም እንቅስቃሴ ነው፣ የሃይማኖት ስብከትም እንቅስቃሴ ነው፣ ራሱ ህይወትም እኮ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ለመኖርም ፈቃድ አውጡ እንዳይባልና “ወይ እቺ አገር!” እንዳንል፡፡

ከስንት ዓመት ይፋ ያልሆነ እገዳ በኋላ በቅርቡ የተፈቀደው የተቃውሞ ሰልፍ የማድረግ ህገመንግስታዊ መብት ይሄ መንግስት ልብ እየገዛ ነው ብለን አመስግነን ስናበቃ፣ ከአንድነት ፓርቲ “አባላቴ ታሰሩብኝ” የሚል ስሞታ መስማት “ምስጋናዬን መልስልኝ” ያሰኛል፡፡ (የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ዳያስፖራዎችን ሲያነጋግሩ፣ “ቢሮክራሲው ቢያስቸግራችሁም ሌላ አማራጭ አገር ስለሌላችሁ አኩርፋችሁ መሄድ አትችሉም፤እዚሁ መታገል እንጂ” ያሉት አፅናናኝ!)
በዚሁ ሳምንት የሰማሁት ሌላ ዜና ደግሞ ምን መሰላችሁ? ጀግናው አትሌታችን ኃይሌ ገ/ሥላሴ ፕሬዚዳንት የመሆን ፍላጎት እንዳለው መግለፁ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ጠ/ሚኒስትር የመሆን ፍላጎት እንዳለው መናገሩ ትዝ ይለኛል፡፡ ያኔ የተፈጠረች አንድ ቀልድ ላውጋችሁ፡፡ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ (ነፍሳቸውን ይማረውና) “ኃይሌ ጠ/ሚኒስትር መሆን እፈልጋለሁ አለ” ተብሎ ይነገራቸዋል፡፡ እሳቸው ምን ቢሉ ጥሩ ነው? “ አይ ኃይሌ! ፖለቲካ እንደ ሩጫ በትራክ ላይ የሚሮጥ መሰለው --- በእሾህ ምንጣፍ ላይ እኮ ነው” (ኮፒራይቱ የህዝብ ነው!) ጠ/ሚኒስትሩ እውነት ብለዋል፡፡ ግን እኮ ኃይሌም ቢሆን በፅናቱ አይታማም፡፡ (“ኢንዱራንስ” የሚል ፊልም እኮ ያለነገር አልተሰራለትም!)
ደግነቱ እሱም ሃሳቡን ቀየረ --- ጠ/ሚኒስትር የመሆኑን ነገር እርግፍ አድርጎ በመተው ሩጫው ላይ ተጋና ዓለምን አጃኢብ ያሰኘ አያሌ ስኬቶችን ተቀዳጀ፡፡ በቢዝነስ መስኩም ዓይናችን እያየ በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርቶ የስኬት ማማ ላይ ጉብ አለ፡፡ ከዚህ ሁሉ በኋላ ነው (ሩጫ ሰለቸው እንዴ?) ሰሞኑን ደግሞ የኢትዮጵያ ርዕሰ ብሔር የመሆን ፍላጎት አለኝ ያለው (በፖለቲካ ፍቅር ተማረከ እንዴ?)
በነገራችሁ ላይ ኃይሌ ፕሬዚዳንት ለመሆን መፈለጉን የቁም ቅዠት ወይም ቀቢፀ ተስፋ ነው የሚል ድፍረት የለኝም፡፡ ለምን መሰላችሁ? ሰውየው ኃይሌ እኮ ነው! ከፈለገ ያደርገዋል፡፡ እስካሁን ያከናወናቸው ተግባራት እኮ የአገር ፕሬዚዳንት ከመሆን የሚልቁ ተግባራት ናቸው፡፡ እሱ ደግሞ አንዴ ከተናገረና ካለመ ወደ ኋላ እንደማይል እኛ ብቻ ሳንሆን ዓለምም ያውቀዋል፡፡

እናላችሁ --- እኔን ያሳሰበኝ “ኃይሌና ፖለቲካ ይስማማሉ ወይ?” የሚለው ነው - የጦቢያን ፖለቲካ ታውቁት የለ! (ያለእዳው ዘመቻ እንዳይሆን ሰጋሁ!) ለዚህም ነው “ የዓለማችን የሩጫ ንጉስ ምን ሲል ፖለቲካን አሰበው?” ብዬ የተጨነቅሁ የተጠበብኩለት፡፡ ከጭንቀቴም ብዛት ለአንድ ወዳጄ አወያየሁት (እኔም እኮ ያለዕዳው ዘመቻ ሆንኩላችሁ) ወዳጄም እንዲህ አለኝ “እሱ እኮ ስማርት ነው ! ፕሬዚዳንት መሆን የፈለገው ከፖለቲካ ለመራቅ አስቦ ነው” ጨርሶ አልገባኝም ፡፡ አሁን ይሄ ምን ይሉት ንግግር ነው አልኩ - በሆዴ፡፡ ወዳጄ ማብራሪያውን ቀጠለበት “አየህ -- በኢህአዴግ አገዛዝ ፕሬዚዳንት መሆን እኮ ነፃነትህን ማወጅ ነው ---ይሄ ሥልጣን በምንም መንገድ ከሃይማኖትም ሆነ ከፖለቲካ አያነካካህም-- ቢበዛ መስከረም ላይ ለፓርላማ የመክፈቻ ንግግር ታደርጋለህ -- የድሮዎቹ ነገስታት ባሳነፁት ውብ ቤተመንግስት ውስጥ ደግሞ ከዓለም ዙርያ የሚመጡ እንግዶችን እየተቀበልክ ታነጋግራለህ -- አልፎ አልፎ የመሰረት ድንጋይ ለማስቀመጥ ትጋበዝ ይሆናል --በተረፈ ግን የራስህ ሆቢ ባይኖርህ እንኳን ከመፃህፍትም ላይ ቢሆን ፈልገህ እዚያ ላይ ማተኮር ነው” አለኝ ኮስተር ብሎ፡፡ ለእኔ ይሻለኝ የነበረው ቢስቅ ነበር፡፡ “ትቀልዳለህ እንዴ” ብዬ እንዳልጠይቀው መንገዱን ዘጋብኝ፡፡
አንዳንድ ሰዎች ግን ሲያሙት ሰምቻለሁ “ፕሬዚዳንትነቱን የፈለገው የጡረታ ዘመኑ መደበርያ ሊያደርገው ነው” በማለት፡፡ ይሄ እንኳን የማይመስል ነገር ነው፡፡ (ሰው እንዴት አገር የመምራት ትልቅ ሃላፊነትን ለመደበርያነት ያስበዋል?)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

ብርዱ እንዴት ይዟችኋልሳ! ምን ይገርምሀል አትሉኝም..ይቺ በየመሀሉ የምትወጣው ድብን የምታደርግ ጸሀይ፡፡ “በረደን!” “አንዘፈዘፈን!” ስንል…አለ አይደል…ሌላ በኩል ጸሀዩዋ… “ገና ታራለህ ትደብናለህ፣ ታዲያ ምን… ትሆናለህ!” የምትለን ይመስላል፡፡ የሰዉ “ታራለህ፣ ትደብናለህ…” አልበቃ ያለን ይመስል!… ስሙኝማ…በኮሚኒስቶቹ ዘመን ነው አሉ… እዛችው የፈረደባት ሩስያ ውስጥ፡፡ እናማ… ለኮሚኒስት ምሁራን አምስት ያልተጻፉ መመሪያዎች ነበሩ አሉ፤ መጀመሪያ ነገር አታስብ፣ ካሰብክ ደግሞ አትናገር፣ ካሰብክና ከተናገርክ አትጻፍ፣ ካሰብክ፣ ከተናገርክና ከጻፍክ ደግሞ አትፈርም፣ ካሰብክ፣ ከተናገርክ፣ ከጻፍክና ከፈረምክ ግን ወዮልህ! እናላችሁ…ዘንድሮ በየቦታው “…ከፈረምክ ግን ወዮልህ!” የተባለ ይመስል አገልግሎት ማግኘት አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡ ስሙኝማ…የሆነ ሰው መታወቂያ ለማውጣት አንድ አገልግሎት መስጫ ይሄድላችኋል፡፡

እዛም ሲደርስ ኮምፒዩተሩ አጠገብ ያለችው ‘ትንሽዬ ልጅ’…አለ አይደል… “ኮምፒዩተሩ አይሠራም…” ትለዋለች፡፡ እሱም አየት ሲያደርግ ኮምፒዩተሩ ፏ እንዳለ ነው፡፡ ሌሎች መታወቂያ ፈላጊዎችም “ኮምፒዩተሩ አይሠራም…” ተብለው ግራ ተጋብተው ቆመዋል፡፡ እናማ…ሰውየው “ይኸው በርቶ ይሠራ የለ እንዴ?” ይላታል፡፡ እሷም ምን ብትል ጥሩ ነው… “አይ፣ አሁን መታወቂያ መሥራት አይቻልማ…” ትለውና “አወቃለሁ ካልክ ለምን አንተ አትሞክርም“” ትለዋለች፡፡ ነገርዬዋ የሹፈት መሆኗ ነው…አጅሬ አልሆን ብሎት ‘ሲንደፋደፍ’ ከጓደኞቿ ጋር ‘ሙድ ሊይዙበት!’ ቂ…ቂ…ቂ… እግረ መንገዴን የሆነች ነገር ትዝ አለችኝማ…ምን የሚል አባባል አለ መሰላችሁ…“ሁሉም ነገር በተበላሸበት ሰዓት ፈገግ የሚል ሰው ችግሩን ማን ላይ እንደሚላክክ አስቦ ወስኗል ማለት ነው፡፡” እና ነገርዬው ሁሉ ሲበላሽ…አለ አይደል… ቲማቲም እንኳን በአቅሟ ሀያ ምናምን ብር ስትገባ ፈገግ የምንል ሰዎች የቲማቲሙን መወደድ ማን ላይ እንደምናላክክ አስበንበታል ማለት ነው፡፡

ቂ…ቂ…ቂ… ታዲያላችሁ…ሰውየው የተወሰነች ደቂቃ ተቀምጦ የአራት ሰዎች መታወቂያ ሠራላችሁና አረፈው! ለካስ ትንሽዬዋ ልጅ ገና መታወቂያ እንዴት እንደሚሠራ አታውቅም ኖሯል! ስሙኝማ…የምር ግን…እንዲህ አይነት ነገሮች ብዙ ቦታ የተለመዱ እየሆኑ ነው፡፡ ምናልባትም ልጆቹ ለታጩበት ሥራ በቂ ‘ኦሪዬንቴሽን’ ስላላገኙም ይሆን ወይም መጀመሪያም ‘ምደባዎቹ’ ችግር ስላለባቸው…አስቸጋሪ ሁኔታዎች እየበዙ ነው፡፡ በዚህ ሁሉ መሀል ‘ሜይንስትሪም ሚዲያ’ የምንለው እዚህ ችግር ላይ ጊዜ ሰጥቶ…“ኧረ መላ በሉ…” አይነት ነገር አለማለቱ ያስገርማል፡፡ ይቺን ስሙኝማ…አንዱ ሌላውን እንዲህ ብሎ ይጠይቀዋል…“በሶቪየት ህብረት ውስጥ ልክ እንደ አሜሪካ አይነት የንግግር ነጻነት አለ?” ሰውየውም እንዲህ ሲል መለሰ፣ “በመርህ ደረጃ አዎ፤ ለምሳሌ አሜሪካ ውስጥ ኋይት ሀውስ ፊት ለፊት ሆነህ ‘ሬጋን ይውደም!’ እያልክ ብትጮህ ምንም አይነት ቅጣት አይደርስብህም፡፡

ሞስኮ ውስጥ በቀዩ አደባባይ ቆመህ ‘ሬጋን ይውደም!’ እያልክ ብትጮህም ምንም ቅጣት አይደርስብህም፡፡” እናማ…በራሳችን የሆነ ‘ቀይ አደባባይ’ ቆመን…“በሰዎች ምደባ፣ ችሎታና ስነ ምግባር ይቅደሙ!” የምንልበት ጊዜ እየናፈቀን ነው፡፡ እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…እንደው ነገረ ሥራችን ሲታይ…አለ አይደል… ከጊዜ በኋላ አዲስ አበባ ምን ልትባል የምትችል መሰላችሁ…“የገጠር አካባቢዎች ወደ ከተማነት እንደሚለወጡ ሁሉ፣ ከተማዎችም ወደ ገጠርነት እንደሚለወጡ ምሳሌ የሆነች…” በየቢሮው፣ በየገበያው፣ በየመንገዱ…የምናሳያቸው ባህሪያት አንዴ ‘ጓድ’ ሌኒን… “አንድ እርምጃ ወደፊት፣ ሁለት እርምጃ ወደ ኋላ” ያለው አይነት ነገር ይሆናል፡፡ ስሙኝማ… ‘ጓድ’ ሌኒንን ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…አንድ አስተማሪ ልጆቹን ሰብስቦ በአንድ መናፈሻ ውስጥ እያዘዋወራቸው ነው፡፡ ልጆቹ ደግሞ የከተማ ልጆች ስለሆኑ አንድም አይነት እንስሳ አይተው አያወቁም፡፡

እናማ… የሆነ ጥንቸል ብቅ አለ፡፡ አስተማሪውም ወደ ጥንቸሉ እያመለከተ “ይሄ ማን እንደሆነ ታውቃላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው፡፡ አንድም አወቃለሁ የሚል ልጅ አልተገኘም፡፡ አስተማሪውም “እንግዲያው እኔ ልጠቁማችሁ” አላቸው፡፡ “በብዙ በምናነባቸው ታሪኮች ውስጥ ይገኛል፣ ብዙ መዝሙሮች ተዘምረውለታል፡ ዜማዎች ተዚመውለታል፡፡ አሁንስ አወቃችሁ?” አላቸው፡፡ ይሄን ጊዜ አንድ ልጅ ጥንቸሉን ቸብ፣ ቸብ እያደረገ ምን አለ መሰላችሁ… “እኔ እኮ መልክህ እንዲህ እንደሆነ አላውቅም ነበር፣ አያቴ ሌኒን…” ብሎት አረፈው፡፡ መዝሙርና ዜማ ማብዛት አንዳንዴ እንዲህ ያደርጋል! እናላችሁ…በየቦታው ያልሆኑትን ‘መስሎ መቅረብ’ በዝቷል፡ የሀብታም ቤት ግንብ የሚያካክል ወንበር ላይ የተቀመጠው ሁሉ ለ‘በርጩማ የሚበቃ’ ያህል የሥራ ችሎታ ላይኖረው ይችላል፡፡ ግን…አለ አይደል…‘ጊዜው’ ሆነና ወንበሩ ላይ እየተሽከረከረ… (እየተሽከረከሩ በዛው ‘ዞሮባቸው’ የቀሩ ልብ እየተባለ…) “ለእግሬ ውሀ አምጡ…” ለማለት የሚዳዳው… በድምር ሳይሆን በብዛት እየተበራከተ ይመስላል፡፡ ‘ኩኩሉው’ የሚል በዝቶ “ነግቷል!” የሚል የጠፋበት አገር እየመሰለ ነው፡፡

እናላችሁ…የከተማዋን የህንጻ መስታወቶች አንጋጠን እያየን… ራሳችንን በመስታወት ማየት የረሳን ሰዎች ቁጥራችን እንደ ችግሮቻችን ቁጥር እያሻቀበ ያለበት ዘመን እየሆነ ነው፡፡ ስሙኝማ…ይቺን ነገር ከዚህ በፊት አውርተናት ነበር መሰለኝ፡፡ እሱዬው ለአንድ ምግብ ከጠቅላይ ግምጃ ቤት ይወሰድ የነበረው በዓመት የሚከፈል የሦስት ወር ደሞዝ የሚጠየቅባቸው ቤቶች… ‘ገርሉካውን’ ይዞ ይገባል፡፡ ሜኑ ይቀርብለታል፡፡ ‘ኳንተም ፊዚክስ’ ምናምን ያጠና ይመስል በተመስጦ ሲያይ ይቆይና ምን ይላል መሰላችሁ…“ይኸው ብቻ ነው?” ይላል፡፡ ሜኑው እኮ ሁለት ገጽ ተኩል ጥቅጥቅ ያለ ነው! “ይኸው ነው…” ብለው ይመልሱለታል፡፡

ከዛ ምን ቢያዝ ጥሩ ነው፡፡ “አንድ የጾም በያይነቱ…” ይልና ወደ ‘ገርሉካው’ ዘወር ብሎ “አንድ ይበቃል አይደል! በልተን ካነሰ ብንጨምር አይሻልም…” ይላታል፡፡ከዛ ደግሞ አጠገቡ የቆመውን አስተናጋጅ ‘አጨብጭቦ ይጠራና’ ቂ…ቂ…ቂ…ምን ይላል መሰላችሁ…“የሚጠጣ ምን አለ?” የመጠጥ አይነት ይዘረዝርለታል፡፡ ወደ እንትናዬዋ ዘወር ይልና “ውሀ ይሻለናል አይደል…” ይልና ለአስተናጋጁ ምን ቢለው ጥሩ ነው… “ውሀ በጆግ አምጣልን፡፡” ‘ኧረ እባካችሁ’ ማስመሰልም አይነት አለው! እናማ… በየቢሮው፣ በየመንገዱ፣ በአገልግሎት መስጫ…ምናምን ቦታዎች የማስመሰል ‘እርፍና’…አለ አይደል…እየበዛ ሲሄድ ጥሩ አይደለም፡፡

አንዱ ጓደኛውን ምን ብሎ ይጠይቀዋል መሰላችሁ…“በካፒታሊስት ተረትና በማርክሲስት ተረት መካካል ያለው ልዩነት ምንድነው?” ጓደኝዬውም ምን ብሎ መለሰ መሰላችሁ…“የካፒታሊስት ተረት ‘ከዕለታት አንድ ቀን…ነበር…’ ብሎ ይጀምራል፡፡ የማርክሲስት ተረት ደግሞ… ‘ከዕለታት አንድ ቀን…ሊኖር ይችላል…’ ብሎ ይጀምራል፡፡ እና… የዘንድሮ ነገረ ሥራችን ላይ… “ከዕለታት አንድ ቀን…” የነበረው ሁሉ እየጠፋ እርግጠኛ ስላልሆንበት ‘ከዕለታት አንድ ቀን’ እያወራን ነው፡፡ እናማ…በዚህ የግብር መክፈያ ወቅት በየቦታው የምናያቸው “ገና ትከስላለህ፣ ትደብናለህ…” አይነት አገልግሎት አሰጣጦች…አለ አይደል… የሚመለከታቸው ክፍሎች (ያሉ ስለሚመስለን…) ይመልከቷቸውማ! ደህና ሰንበቱልኝማ!

Published in ባህል
Saturday, 20 July 2013 10:20

የትግራይ ጉዞ ማስታወሻ

ተናጋሪዋ ምድር
ትግራይ የትራጀዲና ኮሜዲ መድረክ ናት!
ከክርስቶስ ልደት 2006 ዓመት በፊት “አልሙጋህ” የተባለ ጣኦት ይመለክበት የነበረውን አዲአካውህን ጐብኝተን ውቅሮ ስንገባ ነው ጽሑፌን በይደር የቋጨሁት፡፡
ውቅሮ ለጥ ባለ ሜዳ ላይ የተመሰረተች ዘመናዊ ከተማ ናት፡፡ ከዚያች ውብ ከተማ ዳር እንደደረስን የከተማዋ ከንቲባና ነዋሪዎችዋ እንደሌሎች ከተሞች ነዋሪዎች ሁሉ በጭፈራ፣ በሆታና በዕልልታ ነው የተቀበሉን፡፡ ደመቅ ያለ ቁርስም ከቡና ጋር ጋብዘውናል፡፡ እንግዳን በክብር መቀበልና መጋበዝ የትግራዮች ባህል መሆኑን በተደጋጋሚ ስላየን ብዙም ላይደንቅ ይችላል፡፡ ግን የውቅሮ ከተማ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ሊወደሱበት የሚገባ አንድ እንግዳ ነገር ተገንዝበናል፡፡ በውቅሮ ቅዳሜ የሥራ ቀን ነው፡፡ ህዝቡን ለማገልገል ሲባል ሠራተኛው በሙሉ ፈቃደኝነት ቅዳሜን በሥራ እንደሚያሳልፍ ተነግሮን “ይበል በሌሎች የሀገሪቱ ከተሞችም ይለመድ” ብለናል፡፡
የውቅሮ ቆይታችንን በአጭሩ አጠናቀን መጓዝ ስላለብን፣ ወደ አውቶቡሳችን መሰባሰብ ጀምረናል፡፡ ጊዜውም የተሳፈርንበት አውቶቡስም እሽቅድምድም የያዙ ይመስል በየፊናቸው ይከንፋሉ፡፡ አውቶቡሳችን ሲከንፍ ተናጋሪዋን ምድር እየቃኘን፣ በአየነው ተራራ፣ ወይም የተፈጥሮ ጥበቃ እየተደመምን ስንጓዝ ሌላ አስደናቂ ነገር ሲቀበለን፤ በቃ ትግራይ ማለት ቢገልጧት፣ ቢገልጧት ተነብባ የማታልቅ ግዙፍ መጽሐፍ ትመስላለች፡፡
በዚህ አይነት ስንጓዝ ቆይተን በአገራችን ታሪክ የመጀመሪያው ውቅር ቤተክርስቲያን ከሚገኝበት አብርሃ ወአጽብሃ ቀበሌ ደረስን፡፡ አብርሃ በአራተኛው መቶ ክፍለዘመን የአክሱም ንጉሥ የነበረና ክርስትና መንግሥታዊ ሃይማኖት እንዲሆን የደነገገ ነው፡፡ የአብርሃ ወአጽብሐ ቀበሌ በስሙ የተሰየመውም በዚሁ ታሪካዊ ምክንያት ሲሆን መቃብሩም በዚሁ ቤተክርስቲያን ውስጥ ይገኛል፡፡
ስለቤተክርስቲያኑ የአሰራር ጥበብና በውስጡ ስለሚገኙት ቅርሶች፣ ስለ ሶስቱ ቤተመቅደሶች፣ ስለ ቦታው አቀማመጥ፣ ወዘተ ብዙ እጅግ ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ ግን ቦታም ጊዜም የለም፣ እንደ ጉብኝታችን ሁሉ ጽሑፌንም ፈጠን ማድረግ አለብኝ፡፡ አለዚያ ጋዜጣችን ትግራይ ላይ ብቻ ቢከርምም ስለ ትግራይ ምስጢር፣ ስለ ትግራይ ተአምራዊነት ጽፎ መጨረስ አይቻልም፡፡ የገደላትና ተአምራት ፀሐፊዎች እንዲህ አይነቱ እጹብ ድንቅ የሆነ ጉዳይ ሲገጥማቸው “ሰማዩ ሰሌዳ ወይም ብራና፣ የክረምቱ ዝናም ቀለም ቢሆኑም ጽፌ መጨረስ አልችልም” ይላሉ፡፡ የትግራይ ጉዳይ ያለምንም ማጋነን ለእኔ እንዲያ ነው፡፡
አብርሃ ወአጽብሐ ቀበሌ ከታሪካዊው ቤተክርስቲያኗ በተለይ የምትደነቅበት አጋጣሚም ተፈጥሯል፡፡ ቀበሌዋ እጅግ ከተራቆቱት የክልሉ ቀበሌዎች አንዷ ነበረች፡፡ ግን በህዝቡ እንደ ብረት የፀና ትግስትና ጥረት ዛሬ ተቀይራለች፤ ተራሮችዋ በተፈጥሮ ደን እየተሸፈኑ ናቸው፡፡
የአብርሃ ወአጽብሐ ቀበሌ ስም ሲነሳ የአንድ ጀግና አርሶ አደር ስም አብሮ መወሳቱ ግድ ነው፡፡ ስሙ “አባ ሐዊ” ይባላል፡፡ በትግርኛ “አባ እሳት” ማለት ነው፡፡ ትክክለኛ ስሙ ግን ገብረሚካኤል ዓደይ ይባላል፡፡ “አባ ሐዊ” የሚለው ቅጽል ስም የወጣለት በግብሩ ነው፡፡ ሲናገር እሳት ነው፤ ሲሰራ ደግሞ የበለጠ ነበልባል ነው፡፡ ኃላፊዎች ከቢሮአቸው ቁጭ ብለው ወይም ህዝብን ሰብስበው “እንዲህ ብታደርጉ የተሻለ ምርት ታገኛላችሁ፤ ወይም ምርታችሁ እንዲያድግ ይህን ፍጠሩ ማለት የለባቸውም፡፡ እንዲህ ብለው ሲያዝዙ ህዝቡ “የምትነግረን እውነት ከሆነ ለምን አንተ አልከበርህም?” የሚል ጥያቄ ቢያነሳ መልስ የለውም፡፡ ስለዚህ መሪዎች ሠርቶ በማሳየት አርአያዎች እንጂ የወሬ ጀግኖች መሆን የለባቸውም” ብሎናል በኩራት፡፡
አብርሃ ወአጽብሃ ቀበሌ እጅግ ዘግናኝ ከሆነ ድህነትና መራቆት የተራቀቀችው በአባ ሐዊ ፋና ወጊነትና አመራር ሰጭነት መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ አባ ሐዊ በዚህ የልማት ጀግንነቱ በዓለምአቀፍ ደረጃ አንድ ጊዜ፣ በአገር አቀፍ ደግሞ 15 ጊዜ ተሸልሟል፡፡ የአባ ሐዊ የአመራር ጥበብ ቀድሞ ሠርቶ በማሳየት በመሆኑ፣ በህዝቡ ዘንድ ትልቅ አመኔታና ከበሬታን አግኝቷል፡፡
ከአባ ሐዊ ጓሮ ተገኝተን በአይናችን አይተን ያረጋገጥነው እውነትም ይኸው ነው፡፡ ያ አስፈሪ የነበረ ራቁት መሬት በደን ከመሸፈኑም በላይ ልዩ ልዩ አትክልቶችና ፍራፍሬዎች ተንዠርግገው ይታያሉ፡፡ የሰው ልጅ ከፈለገ አጥፊ ከፈለገ ደግሞ ተፈጥሮን ከነሙሉ ለዛዋና ክብሯ ሊመልሳት እንደሚችል መልካም አብነት ነው፡፡
ከአባ ሐዊ ጓሮ የተንዠረገጉትን ልዩ ልዩ አትክልትና ፍራፍሬዎችን በአድናቆት ከጐበኘን በኋላ ወደ እንግዳ መቀበያው ወሰደን፡፡ የእልፍኝ ቅርጽ ካለው እንግዳ መቀበያ ቤቱ ቁጭ እንዳልን፣ በሚያስገርም ፍጥነት ሻሽ የመሰለ ማር በዳቦ እያደረገ ለእያንዳንዱ ተጓዥ አደለ፡፡
ጠንክረው ከሰሩ ጣፋጭ ውጤት እንደሚገኝ ከአባ ሐዊ ተምረን፣ አመስግነንም ጉዟችንን ቀጠልን፡፡ አክሱም ገብተን ማደር ስላለብን እንጂ ልክ እንደ ማሩ ሁሉ ያንን የሚጣፍጥ አንደበቱን እያዳመጥን ትንሽ ጊዜ ብንቆይ ደስታውን አንችለውም ነበር፡፡
የጥበብ ተጓዦች ጉዞ ከጀመሩበት ዕለት አንስተው በአውቶቡሱ ውስጥ መዝፈን፣ ማቅራራትና መዘመር ወይም ግጥምና ዜና በማንበብ ራሳቸውን ማዝናናት የተካኑበት ቢሆንም ከአብርሃ ወአጽብሐ ቀበሌ ጉብኝታቸው በኋላ ግን የሆነ ህመም የያዛቸው ይመስል እየፈዘዙ መጡ፡፡
እርግጥ ነው ትግራይ ግራ ታጋባለች፤ ትግራይን ከራስ እስከ እግሯ ሳይጐበኙ “ኢትዮጵያዊ ነኝ” ማለትም ይከብዳል፡፡ ወይም ያሳፍራል፡፡ ትግራይ ተራራዋ ሁሉ፣ ከርሰምድሯ ሁሉ፣ ገዳሟ መስጊዷ ሁሉ የአገሪቱን ወይም የመላ አፍሪካን ምስጢር ደብቀው ይዘዋል፡፡
ጉዟችን ቀጥሏል፡፡ መንገዱ ገና እየሰፋ ስለሆነ ኮረኮንች ነው፡፡ በአብርሃ ወአጽብሐ ቀበሌ ህዝብ ጥንካሬ፣ በአባ ሐዊ የአመራር ስልት፣ በገዳሙ ጥንታዊነት ድንቅ ጥበብ እየተደነቅን ስንጓዝ በስተግራ በኩል እውቅ ቀራጺ ተጠንቅቆ ያዘጋጀው የሚመስሉት የገርዓልታ ሰንሰለታማ ተራሮች ከፊት ለፊታችን ድንቅ አሉ፡፡ ተራሮቹ እንደ ማንኛውም ተራራ የድንጋይ ቁልሎች አይደሉም፡፡ ይልቁንም ከአፍ እስከ ገደፋቸው የአገራችን የሥልጣኔ፣ የታሪክ፣ የሥነ ጥበብ፣ የሥነ ሕንፃና የሥነ ፈለክ ምስጢሮች የታጨቁባቸው የምስጢር ጐተራዎች ናቸው፡፡
አስደናቂውን የአባ ቶምዓታን ቤተክርስቲያን ጨምሮ በአብዛኞቹ ተራሮች ላይ ከ34 በላይ ከአንድ አለት የተፈለፈሉ አብያተክርስቲያናት አሉ፡፡ እያንዳንዳቸውን ጐብኝቶ ለመጨረስ ቢያን ለአንዱ ቤተክርስቲያን የአንድ ቀን ቆይታን ይጠይቃል፡፡
በገርዓልታ ተራሮች ተፈጥሮአዊ አቀማመጥ፣ በውስጣቸው ስላሉ ምስጢራት እየተደነቅን በመጓዝ ላይ ሳለን ከፊት ለፊታችን፤ ግን በርቀት አስደናቂው እና በር አልባው የደብረዳሞ ተራራ በኩራት ተጀንኖ ታየን፡፡
ደብረ ዳሞ በ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አባ አረጋዊ የሚባሉ መነኩሴ የመሠረቱትና እንደ ግዑዝ ነገር በመጫኛ ብቻ እየተጐተቱ የሚወጡበት ታላቅ ደብር ነው፡፡ የመጐብኘት ዕድሉ ስላልነበረን ውስጤ እያዘነ ግን ደግሞ በካሜራዬ ምስሉን ለማስቀረት እየሞከርኩ ማለፍ ግድ ሆነ፡፡ ጥላሁን ገሠሠ “በዓይን እየተያዩ የመናፈቅ ጣጣ…” ያለው እንዲህ አይነቱ የውስጥ ስቃይ ገጥሞት ይሆን?
ትግራይ የሃይማኖት፣ የስልጣኔ፣ የፍልስፍና፣ የዕውቀትና የማንነት ምስጢራት ዋሻ ብቻ ሳትሆን የትራጄዲና ኮሚዲ መድረክም ናት፡፡ አሁን ደግሞ ሐውዜን ገባን፡፡ ሐውዜን መራራ ትራጄዲ ከተተወነባቸው መድረኮች አንዷ ናት፡፡ በቀድሞው መንግሥት የጦር አውሮፕላኖች በአንድ የገበያ ቀን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጐች እንደ ቅጠል ረግፈውባታል፡፡
የትራጄዲውን መድረክ ሐውዜንን በሀዘን ተሰናብተን ወደፊት እየተጓዝን ነው፡፡ ትግራይ ክልል ውስጥ ተራራ ላይ ቢወጡ አስደናቂ ጥበብ ይነበባል፤ መሬቱን ቢቆፍሩ እጅግ የሚገርም ምስጢር ይገኛል፡፡ ስለሆነም ማየት ያለብን ብዙ ነገር ቢኖርም በጊዜ አክሱም ለመግባት መፍጠን ይጠበቅብናል፡፡ ግን ደግሞ ውቧን ከተማ አድግራትን ማግኘት አለብን፡፡
አድግራትም የተለመደው ህዝባዊና ደማቅ አቀባበል ከምሳ ግብዣ ጋር ተደረገልን፡፡ ምሳው ደግሞ ከሚጣፍጠው የትግራይ ባህላዊ ምግብ “ጥህሎ” እና ከንፁህ የማር ጠጅ ጋር ነበር፡፡ በነገራችን ላይ “አድግራት” ማለት “አድገራሕት” ማለትም “የእርሻ አገር” ማለት መሆኑን አቶ ከበደ አማረ አስረድተውናል፡፡ ለጥ ካለ ሜዳ ላይ የተመሰረተች በመሆኗ እውነትም ለእርሻ ምቹ የነበረች መሆኗን መገንዘብ አያዳግትም፡፡
አድዓራት ውብ ከተማ ናት፡፡ የዩኒቨርሲቲው መመሥረት ከሻዕቢያ ጦርነት በኋላ ተቀዛቅዛ የነበረችውን ከተማ አነቃቅቷል፡፡ የአድግራት ከተማ ባለሥልጣናትና ነዋሪዎችን ግብዣ አጠናቀን በምስጋና ተሰነባበትንና ጉዟችንን ቀጠልን፡፡ የእኛ ነገር መሄድ፣ ማየት፣ ባየነው ነገር መደነቅ ነው፡፡ ድካም የሚባል ነገር የለም፡፡ ከሁሉ የሚገርመኝ የ78 አመቱ አዛውንት አቶ አስፋው ዳምጤ የእግር ጉዞን የሚጠይቁ ታሪካዊ ቦታዎችን ለመጐብኘት ከወጣቶች እኩል፤ ብዙ ጊዜ ግን ቀድመው ሲራመዱ ማየት የትግራይ መስህብ ቦታዎች ምን ያህል ጉጉት ፈጣሪዎች እንደሆኑ ያስረዳል፡፡
ወደፊት እየገሰገስን ነው፡፡ ከፊትለፊታችን ደግሞ የዓለም ጥቁር ህዝቦች ብቻ ሳይሆኑ ራሳቸው ጣሊያኖች በወርቅ ቀለም ብዙ እጅግ ብዙ ቁምነገሮችን የጻፉለት አድዋ ይጠብቀናል፡፡ ጊዜው ግን ከእኛ ፈጥኖ እየተጓዘ ነው፡፡ የአክሱም ከተማ ከንቲባ አቶ አበራም ህዝቡን አሰልፈው እየጠበቁን ነው፡፡ ስለዚህ ዝነኛዋን አድዋን በዝምታ አልፈን፣ ስንመለስ በደንብ ልንጐበኛት ቀጠሮ ይዘን ወደ አክሱም ገሰገስን፡፡
ጉዞ ወደ አክሱም ማለት ደግሞ ወደ ጥንተ ታሪክ፣ ወደ ማንነታችን መፍለቂያ በከፍተኛ ጉጉት መጓዝ ማለት ነው፡፡ በተለያዩ ጽሑፎችና ምስሎች አይተን የምንጓጓላትን አክሱምን ልናያት፣ አይተንም በአግባቡ ልናውቃት ነው፡፡ ግን ጊዜው ከእኛ ጋር እልህ የተጋባ ይመስል ይከልባል፤ እነሆ 1፡30 ሆነ፡፡
እናም የናፈቅናትን አክሱምን ሌባ ይመስል በጨለማ ገባንባት፡፡ ለብዙ ሰዓታት ሲጠብቁን የቆዩት የከተማዋ ባለሥልጣናትና ህዝቡም እስከዚህ ሰዓት ድረስ በከፍተኛ ትዕግስት ሲጠብቁን አምሽተው ነበርና በክብር ተቀበሉን፡፡ ሞቅ ያለ ራት ከጋበዙን በኋላ ወደተያዙልን ሁለት ሆቴሎች አመራን፡፡ በየደረስንበት ቦታ ሁሉ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ “እኔም ከጥበብ ተጓዦች ጐን አልለይም” ብሎ ሲከተለን እንደነበር በዚህ አጋጣሚ መግለጽም ማመስገንም እፈልጋለሁ፡፡ አክሱምን ሲነጋ በደንብ እናያታለን፡፡

 

Published in ህብረተሰብ

*ለሌቦቹ ሥጋት እስካልሆኑ ድረስ ንብረትዎትን ተደራድረው ይገዙታል
*ለፖሊስ የሚደረግ የስልክ ጥሪን የሚያውቁበት መላ ግርታን ፈጥሯል
*ከመኪናዎ የተሰረቀ እቃ ታርጋው ተፅፎበት እርስዎን ይጠብቃል
*በክረምት የመኪና እቃዎች ስርቆትና ገበያ ይደራል!

የልደታ ፍርድ ቤትን አጥር ታከው ከተኮለኮሉት መኪኖች መካከል ያቆማት ወያኔ ዲኤክስ መኪናው በአስተማማኝ ስፍራ ላይ በመሆኗ ስጋት አልገባውም፡፡ ለጥብቅና ስራው ወደዚህ ስፍራ አዘውትሮ በሚመላለስበት ጊዜ ሁሉ መኪናውን የሚያቆማት እዚሁ የተለመደ ቦታ ላይ ነው፡፡ የችሎት ቀጠሮውን ጨርሶ ሲወጣ፣ ሰዓቱ 4፡20 ይላል - ከረፋዱ፡፡ ከአንድ ደንበኛው ጋር ቀጠሮ ስለነበረው እየተቻኮለ ከፍርድ ቤቱ ግቢ ወጣና ወደ መኪናው አመራ፡፡ አካባቢው በወትሮው እንቅስቃሴ እንደ ደመቀ ነው፡፡ ሁሉም ነገር ሰላም ይመስላል፡፡ የመኪናው የግራና የቀኝ መመልከቻ መስታወት (ስፖኪዮ) አለመኖሩን እንኳን ልብ ሳይል በሩን ከፈተው፡፡ ዳሽ ቦርዱ፣ የነዳጅ ጌጁ፣ የመኪናው ቴፕ፣ ስፒከር፣ የወንበር ትራሶች፣ የዝናብ መጥረጊያው… ወላልቆ ተወስዷል፡፡ ደነገጠ፡፡
የተቆለፈ መኪናውን ከፍቶ መግባቱን እርግጠኛ ነው፡፡ ግራ ገባው፡፡ “ሌላ መኪና ውስጥ ይሆን እንዴ የገባሁት?” ሲል ራሱን ተጠራጠረ፡፡ ከመኪናው ወርዶ ታርጋውን አየው - የራሱ ነው፡፡ በሰላም ከቤቱ ይዟት ወጥቶ ያቆማት መኪናው፣ በሰአታት ልዩነት ቀፎዋን የቀረችበት ምክንያት አልገለጥልህ አለው፡፡ ትንሽ ሲረጋጋ በመኪና ሽያጭ ሥራ ላይ ለተሰማራውና በጣም ለሚቀርበው ጓደኛው ደውሎ የሆነውን ሁሉ ነገረው፡፡ ጓደኛው ድርጊቱ የተፈመበትን ሰአትና ቦታ ጠይቆት፣ “ደውዬ ላጠያይቅና መልሼ እደውልልሀለሁ” ብሎ ስልኩን ዘጋው፡፡ በአካባቢው ያገኛቸውን ሊስትሮዎች ስለጉዳዩ ቢጠይቃቸውም “ዓይናችንን ግንባር ያድርገው” ብለው እስከመማል ደረሱ፡፡
በዚህ መሀል ጓደኛው ደወለና ዕቃው ሊገኝ ይችላል የሚላቸው ቦታዎች ሁሉ አጠያይቆ “ገና አልገባም” እንደተባለ ነገረው፡፡ “የት ነው የሚገባው?” ጠበቃው ግራ ተጋብቷል፡፡ “ሱማሌ ተራ” አለው ጓደኛው፡፡ የመኪና ዕቃዎች በተሰረቁበት ቅፅበት ወደ ሱማሌ ተራ እንደሚሄዱና በቅናሽ ዋጋ ለባለንብረቱ ለራሱ ወይንም ለሌሎች ፈላጊዎች እንደሚሸጡ ገለፀለት፡፡

እሱም የጠፉበትን ዕቃዎች ለማግኘት ለጥቂት ሰአታት መታገስ እንደሚገባው አስረዳው፡፡ “ምን ማለት ነው? ሌባው ጊዜ አግኝቶ እስኪሰወር ወይም እስኪጠፋ ወይም ዕቃውን እስኪያሸሽ መጠበቅ አለብህ ነው የምትለኝ? ቶሎ ጉዳዩን ለፖሊስ ማሳወቅ ይኖርብኛል ህግ ያወቀው ነገር ጥሩ ነው” አለ ጠበቃው፡፡ ጓደኛው በጠበቃው ምላሽ አልተደሰተም ግን ደግሞ የፈቀደውን ነገር እንዳያደርግ መከልከል አልፈለገም፡፡ ሆኖም የጠፉበትን ዕቃዎች ማግኘት የሚችለው ለፖሊስ በማመልከት ሳይሆን፣ ከሌቦቹ ጋር በመደራደር መሆኑን ነገረው፡፡ ይሄን ጊዜ ጠበቃው ሌላ ዘዴ አሰበ፡፡

ሌቦቹን በትእግስት በመጠባበቅ ለድርድሩ ሲያገኛቸው በፖሊስ ለማስያዝ ወሰነ፡፡ ለጓደኛውም በሃሳቡ መስማማቱንና በትእግስት መጠበቅ መምረጡን ገለፀለት፡፡
ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ጓደኛው ደወለለትና፣ ሰዎቹ ደውለው ዕቃው ገብቷል እንዳሉት ነገረው፡፡ “ለድርድሩ ያመች ዘንድ ስልክ ቁጥርህን ልስጣቸው ወይ?” ብሎ ፈቃዱን ጠየቀው፡፡ ጠበቃው አላቅማማም፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ በመስመር ስልክ ሞባይሉ ላይ ተደወለለትና፣ የመኪናው ታርጋ ተነገረው፡፡ አዎ ሲል አረጋገጠ፡፡ የጠፋበት ዕቃ በሙሉ መግባቱንና 3ሺህ ብር ይዞ 11 ሰዓት ላይ በኒን መስጊድ በራፍ ላይ እንዲገኝ ትዕዛዝ ደረሰው፡፡ ዕቃውን ከማግኘቱ በፊት ገንዘቡን ስፍራው ላይ ለሚጠብቀውና መጥቶ ለሚያናግረው ሰው መስጠት እንዳለበት ጥብቅ ማሳሰቢያ ተሰጠው፡፡ ከዚህ ውጪ የሆነ ተግባር እፈፅማለሁ ብሎ ከሞከረ ግን ዕቃዎቹን እስከ መጨረሻው እንደማያገኝም ተነገረው፡፡
አሁን ለፖሊስ ለማመልከት በቂ መረጃ እንዳለው ጠበቃው ተማምኗል፡፡ ጉዳዩን ለፖሊስ ጣቢያ አመለከተና የተደወለበትን ቁጥር ለፖሊሶች ሰጠ፡፡ ፖሊሶቹ በቁጥሩ ለመደወል ሞከሩ፡፡ ግን ምላሽ የለም፡፡ ደዋዮቹ የተጠቀሙት የመንገድ ላይ ስልኮችን እንደሆነ ፖሊሶቹ ነገሩትና በጣም እየተገረመ የመርማሪ ፖሊሶቹን ቁጥር ተቀብሎ ወጣ፡፡
ልክ እግሩ ከጣቢያው እንደወጣ ስልኩ ጮኸ፡፡ ሌላ የመስመር ስልክ ጥሪ ነበር፡፡ ደዋዩ ቀደም ሲል ቀጭን ትእዛዝ የሰጠው ሰው መሆኑን በድምፁ ለይቶታል፡፡ ከስምምነታቸው ውጭ ጉዳዩን ለፖሊስ ሪፖርት በማድረጉ፣ ለተጨማሪ ወጪ እንደዳረጋቸውና ይህንን ተጨማሪ ወጪ ለመሸፈን 2ሺ ብር በመጨመር፣ 5ሺህ ብር ይዞ በሰአቱ እንዲገኝ ተነገረው፡፡ ጠበቃው እጢው ዱብ አለ፡፡ “እንዴ ለፖሊስ ሪፖርት ማድረጌን ለማን ተናገርኩ?” ሲል ራሱን መመርመር ያዘ፡፡ ለማንም ትንፍሽ አላለም፡፡ ሌቦቹ ዝም ብለው ሊያስፈራሩት እየሞከሩ እንደሆነ አሰበ፡፡ ለሁሉም በቀጠሮው ቦታ ላይ በመገኘት ጉዱን ለማየት ጓጓ፡፡ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ደውሎ፣ ሌቦቹ ሪፖርት ማድረጉን ማወቃቸውን ተናገረ፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ በተለመደው የመስመር ስልክ ጥሪ ተደረገለት፡፡ “ሃሎ” አለ ጠበቃው፡፡ በደጋሚ ሪፖርት ማድረጉ እጅግ እንዳናደደው በመግለፅ “ካንተ ጋር ድርድሬን አቋርጣለሁ፣ እቃህንም አታገኛትም” ሲል ደዋዩ አምባረቀ፡፡

አሁን ጠበቃው እጅግ ደንግጧል፡፡ ምንድነው እየተካሄደ ያለው? ማነው መደወሌን የሚነግራቸው? ግራ ቀኙን እየተገላመጠ የሰማው ሰው እንዳለ ፍለጋ ያዘ፡፡ ደዋዩ ስልኩን ከመዝጋቱ በፊት ግን “የመጨረሻ እድል ሰጥቼሀለሁ” ሲል የመገናኛ ቦታና ሰአቱን ቀይሮ ነገረው፡፡ ከ30 ደቂቃ በኋላ በላይ ተክሉ ኬክ ቤት አካባቢ ተባለ፡፡
አሁን ጠበቃው ወሰነ፡፡ ከ10 ሺ ብር በላይ ቢያወጣ እንኳን የማያገኛቸውን የመኪና ዕቃዎች ከሌባው ጋር ተደራድሮ መግዛቱ አማራጭ የሌለው ጉዳይ እንደሆነ ተረዳ፡፡ ከዚህ በኋላ ለፖሊስ ማሳወቁ አስፈላጊ አለመሆኑን አምኗል፡፡ እናም መኪናውን አስነስቶ ወደተባለው ስፍራ ከነፈ፡፡ ገና መኪናውን ከማቆሙ አንድ ቀጭን ወጣት ወዳለበት መጥቶ ሰላም አለው፡፡ አካባቢው በዚህ ወጣት ግብረ አበሮች ቅኝት ወስጥ መሆኑን ጠበቃው ተገንዝቧል፡፡ “ዕቃው የታለ?” ጠየቀው ወጣቱን፡፡ ሂሳቡን በቅድሚያ መክፈል እንደሚገባውና “5ሺህ ብር ተቀበል” ተብሎ መላኩን ጭምር ነገረው፡፡ “ኧረ የለኝም፡፡ 3ሺህ ብር ብቻ ነው ያለኝ” ጠበቃው ተማፀነ፡፡
“እኔ አላውቅም፣ ተቀበል የተባልኩትን ብቻ ነው የምቀበልህ” አለው፡፡ “ኧረ ባክህ ደውልና ችግሬን አስረዳልኝ፣ ያለችኝ ይቺው ናት” ለመነው፡፡ እያቅማማ ደወለና፣ አለቆቹ አንዱን ሺህ ብር ቅናሽ እንዳደረጉለት ነገረው፡፡ ጠበቃው በዚህ ተስማማ፡፡ ግን ደግሞ ስጋት ገባው፡፡ ይህ ወጣት አራት ሺ ብሩን ተቀብሎኝ በዛው እብስ ቢልስ ሲል ተጠራጠረ፡፡ ለዚህ ችግር ግን የሱማሌ ተራዎቹ “ሰዎች” መፍትሄ አላቸው፡፡ ጠበቃው ገንዘቡን ቆጥሮ ለወጣቱ ሲሰጠው፣ ከበስተጀርባው ሌላ ወጣት የተሰረቁትን ዕቃዎች በሙሉ በኩርቱ ፌስታል ይዞ ቆሟል፡፡ በዛችው ቅፅበት ዕቃዎቹን አስረከበው፡፡ የመኪናው ታርጋ ቁጥር ኩርቱ ፌስታሉ ላይ ተፅፏል፡፡ ከፍቶ ማየት ፈራ፡፡ ዕቃውን የኋላ ወንበሩ ላይ ወርውሮ መኪናውን አስነስቶ ተፈተለከ፡፡ ንዴት፣ እልህ፣ ግራ መጋባት --- ምስቅልቅል ስሜት ተጫጫነው፡፡ በአካባቢው ህገወጥነት ምን ያህል እንደነገሰ እያሰበ ነበር ሱማሌ ተራን ለቆ የወጣው፡፡
ይህ መሰሉ ታሪክ በሶማሌ ተራ የተለመደና የእለት ተእለት እንቅስቃሴ ነው፡፡ የሶማሌ ተራ ህልውና የተመሠረተው ከየስፍራው እየተሰረቁ በሚመጡ የመኪና ዕቃዎች ሽያጭ ላይ ነው፡፡ አካባቢው በጠራራ ፀሃይ የመኪና ዕቃዎቻቸውን ተዘርፈው ለድርድር በሚመጡ፣ ከአገልግሎት ውጪ የሆነባቸውን መኪና ለእርድ ለመሸጥ በሚያስማሙና የተሰረቀባቸውን መኪና ከመበታተኑ በፊት በነፍስ ለማትረፍ በሚጣደፉ ሰዎች የተጨናነቀ ነው፡፡ ሱማሌ ተራ የተመሰረተውም ሆነ ስያሜውን ያገኘው ቀደም ባሉት ዘመናት በአካባቢው በሚሰባሰቡና በሚገበያዩ የሱማሌ ክልል ነጋዴዎች እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ከበኒን መስጊድ ጀምሮ እስከ ተክለሃይማኖት አደባባይ፣ ጌሾ ግቢና አሜሪካን ጊቢን አካሎ የሚገኘው ይኸው አካባቢ፣ ቀስ በቀስ የንግድ ስፍራ በተለይም ከአገልግሎት ውጪ የሆኑ የመኪና ዕቃዎች የሚሸጥበት ቦታ እየሆነ መጣ፡፡ ከአሮጌ መኪኖች የሚፈታቱ ዕቃዎችን በአነስተኛ ዋጋ ለመግዛት ብዙዎች ሱማሌ ተራን ይጐበኟት ጀመር፡፡ የአሮጌ ዕቃዎች ፈላጊው ቁጥር መበራከት በሽያጭ ሥራ ላይ ለተሰማሩት ነጋዴዎች ውጥረት ሆነባቸው፡፡ አቅርቦቱና ፍላጐቱ አልመጣጠን አለ፡፡ ይህንን ሁኔታ ልብ በለው የተገነዘቡት ከተፎዎቹ የሱማሌ ተራ ዕቃ አቅራቢዎች፣ የደንበኞቻቸውን ፍላጐት ለማሟላት ጥረት ማድረጋቸውን ቀጠሉ፡፡ ከአሮጌ መኪና ዕቃዎች በተጨማሪ ከአዳዲስና ዘመናዊ መኪኖች ላይ እየተሰረቁ የሚመጡትን ዕቃዎች ከሌቦች ላይ በመግዛት ለሽያጭ ያውሉት ጀመር፡፡

የተሰረቁ ዕቃዎች ሽያጩ በድብቅ ይካሄድበት የነበረው ያ “ደግ ዘመን” አልፎ፣ ዛሬ በአደባባይ በጠራራ ፀሐይ የተሰረቁ የመኪና ዕቃዎች በአደባባይ በግልፅና በድርድር የሚሸጥበት ጊዜ ላይ ተደረሰ፡፡ አካባቢው የራሱ ያልተፃፈ መተዳደሪያ ህግና መመሪያ ያለው፣ ህገወጦች የነገሱበት፣ በመኪና ሥርቆት የወንጀል ተግባር ላይ ተሰማርተው የከበሩና ቢጠሯቸው የማይሰሙ “ባለሀብቶች” የሚገኙበት፣ ያቆሙት መኪና በጠራራ ፀሐይ ተፈታተው ዕቃዎቻቸው የተሰረቁባቸው ባለንብረቶች ከሌቦች ጋር በሰላማዊ ድርድር የተሰረቁ ዕቃዎቻቸውን የሚገዙበት ስፍራ ነው፡፡ በእርግጥ በሐቀኝነትና በህጋዊ መንገድ የሚገዟቸውን የወላለቁ የአሮጌ መኪና ዕቃዎች፣ በአነስተኛ ዋጋ ለተጠቃሚው የሚያቀርቡ ህጋዊ ነጋዴዎች ሱማሌ ተራ ፈፅሞ የሉም ማለት አይቻልም፡፡
የሱማሌ ተራ ሰዎች በተራ ሌብነት ወይም በጠራራ ፀሐይ ዘራፊነት ብቻ መፈረጁ “ፍትሃዊ” አይመስልም፡፡ እነሱ ከዚያም በላይ ናቸዋ፡፡ የራሳቸው ብቻ መግባቢያ ቋንቋና ምልክት ያላቸው፣ ፖሊስን ከሩቁ ማነፍነፍ የሚችል ልዩ አፍንጫ የተቸሩ፣ የሰረቁትን ንብረት ለባለቤቱ መልሶ የማስገዛት ልዩ ምትሃት የተካኑ “ጥበበኞች” ናቸው፡፡ በርካታ ሰዎች ሳይወዱ በግድ ለሱማሌ ተራ ያልተፃፈ “ሕግ” ተገዝተው፣ የተሰረቁ የመኪና ዕቃዎቻቸውን ከሌቦቻቸው ጋር ተደራድረው ገዝተው ይሄዳሉ፡፡ እንዴት? ለምን? የሚሉ ጥያቄዎች ሱማሌ ተራዎች ጋር አይሰሩም፡፡
እንዲህ እንደ አሁኑ በክረምት ወራት ላይ የሱማሌ ተራ ገበያ ይጧጧፋል፡፡

የተሰረቁ ዕቃዎቻቸውን ፍለጋ አካባቢውን የሚጐበኙ በርካታ “ደንበኞች” ባብዛኛው የመጡበትን አሳክተው ይመለሳሉ፡፡ “እንዴት ከህገወጦች ጋር እደራደራለሁ” በማለት ጉዳያቸውን ለፖሊስ ያመለከቱ ጥቂቶች ደግሞ በሱማሌ ተራዎቹ ሰዎች እልህ አስጨራሽ ቀጠሮ የማያገኙትን ዕቃ ጥበቃ ይባዝናሉ፡፡ የሶማሌ ተራዎቹ ሰዎች ፖሊስ የገባበትንና ክትትል ማድረግ የጀመረበትን ዕቃ ለባለቤቱ በፍፁም አይሸጡለትም፡፡ ድርድር ጀምረው ከነበረም አቋርጠው የዕቃዎቹን ደብዛ ያጠፉታል፡፡
ቴዎድሮስ አያሌው አዲሱ ገበያ አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ግቢ ውስጥ አቁሞ የተሰረቀውን የመኪና ዕቃ ለማግኘት ሳምንታት የፈጀ ጥረት ቢያደርግም አልተሳካለትም፡፡ ንብረቱ መሰረቁን እንዳወቀ ክትትል እንዲደረግለት ለፖሊስ አመለከተ፡፡ ዕቃህን እናገኝልሀልን በሚሉ ደላሎች አማካኝነት በየጊዜው በስልኩ ላይ እየተደወለ የዋጋ ድርድር ሲያደርግ ቢቆይም፣ ዕቃውን ፈፅሞ ማግኘት አልቻለም፡፡ “ሰዎቹ” ደውለውለት ካንተ ጋር “አበድን” ብለውታል፡፡
በሱማሌ ተራ ሌቦቹ (የመኪና አውላቂዎቹ) እና ዕቃ አቅራቢዎቹ (ሻጮቹ) አይተያዩም፡፡ በመሀል ያሉና ሁለቱን ተፈላላጊዎች የሚያገናኙ ደላሎች እንደ አሸን ናቸው፡፡ በዚሁ አካባቢ ያሉ አንዳንድ “ነጋዴዎች” ለመኪና ስርቆት ሥራው ስምሪት ሰጪዎችም ናቸው፡፡ ነጋዴዎቹ ከደንበኞቻቸው የሚቀርብላቸውን የመኪና ዕቃ (በሞዴልና በአይነት ይለያያል) ጥያቄ በቀጥታ በደላሎቹ በኩል ለሌቦቹ እንዲደርሳቸው ያደርጋሉ፡፡ የዲኤክስ ዳሽቦርድና ትራሶች፣ የፋይቭ ኤል ጌጅ፣ የኤክስኪዩቲቭ ስፖኪዮና ዝናብ መጥረጊያ…. ትእዛዙ በቀጥታ ይተላለፋል፡፡ ትእዛዝ ተቀባዩ “ዕቃ አቅራቢ” የተሰጠውን ትእዛዝ ተቀብሎ “ለሥራ” ይሰማራል፡፡ የተሰጠውን ትእዛዝ የሚያሟሉ መኪኖች የት አካባቢ እንደሚገኙ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡
ከአትላስ ሆቴል እስከ ቦሌ ድልድይ፣ ከሜክሲኮ እስከ ብሔራዊ፣ ከፒያሳ እስከ አራት ኪሎ፣ ከሰባራ ባቡር እስከ መድሃኒያለም ት/ቤት ከተማውን ያካልላል፡፡ የተፈለገው መኪና ከተገኘ፣ የተባለውን ዕቃ ለማግኘት ጥቂት ደቂቃዎች ብቻ ይበቃሉ፡፡ በሰለጠነበት የመፈታታት ሙያው ዕቃዎቹን ፈታቶ በፌስታል ይከትና እብስ ነው፡፡ በዚህችው ቅፅበትም ዕቃዎቹን ይዞ ወደ ሱማሌ ተራ ይከንፋል፣ ምክንያቱም ዕቃውን አዘው የሚጠባበቁ ደንበኞች አሉና፡፡ አንዳንዴ መኪናዋን ከነነፍስዋ ሰርቆ እስከማምጣት የሚያደርስ ድርድር ሁሉ ሊፈፀም ይችላል፡፡ እንደውም ይኸኛው እንደሚቀላቸው ይናገራሉ - የሱማሌ ተራዎቹ “ሰዎች” መኪናቸው ከቆመችበት ከነነፍስዋ ተወስዶባቸው እምጥ ትግባ ስምጥ ባለማወቅ ሲባዝኑ ኖረው፣ ተስፋ ቆርጠው የቀሩ፣ መኪናቸው እንደ ቅርጫ ሥጋ ተበልታና ተቆራርጣ ቀፎዋን ያገኙ በርካቶችን ቤት ይቁጠራቸው፡፡
ስዩመ ታደሰ ይህንን የሱማሌ ተራንና የመኪና ዕቃ ስርቆትን ትስስር የሚያወጋው ከራሱ ገጠመኝ ተነስቶ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ብሔራዊ ቲያትር ፊት ለፊት ያቆማት ራቫ ፎር መኪናው ወላልቃ ቆየችው፡፡ ሁኔታው እጅግ ቢያበሳጨውም መፍትሄው እቃው ከሌቦቹ እጅ ሳይወጣ ፈጥኖ አግኝቶ መግዛት እንደሆነ በመረዳት ወደ ሱማሌ ተራ አቀና፡፡ የመኪናዋን ታርጋ በማየት ዕቃው ከጥቂት ሰአታት በፊት እንደገባ የተረዱት ደላሎች፣ ዋጋ ይደራደሩና 2800 ብር ከፍሎ ዕቃውን ይሰጡታል፡፡ ተሰረቀብኝ ካላቸው ዕቃዎች ውጭ የሰጡትን ሌሎች ንብረቶችን “ይሄ የእኔ አይደለም” ብሎ ሊመልስላቸው ቢሞክር፣ “ሰውዬ ዝም ብለህ ይዘህ ሂድ፣የራስህ ነው” ተባለና ይዞ ወደ ቤቱ ሄደ፡፡

ቤቱ ደርሶ የሆነውን ሁሉ ለሚስቱ ሲያጫውታት እጅግ ደነገጠች፡፡ ጠዋት እሷን መ/ቤቷ በራፍ ላይ አድርሷት ሲለያዩ፣ ለእናቷ ከውጭ አገር በውድ ዋጋ ተገዝቶ የመጣላቸው መድሃኒቶችን መኪናው ኪስ ውስጥ በፌስታል እንደታሰረ ማስቀመጧን ነገረችው፣ ኪሱ ሲከፈት ባዶ ነበር፡፡ ድንገት አንድ ነገር ትውስ አለው፡፡ ለሶማሌ ተራዎቹ ሰዎች “የእኔ አይደለም” ብሎ ሊመልስላቸው ሲሟገት የነበረውን ዕቃ ከፌስታል ውስጥ አወጣው፡፡ ባለቤቱ ፊቷ በደስታ በራ፡፡ ባልም እንዲህ ሲል አሰበ “ሶማሌ ተራዎች የሰው ዕቃ አያጐድሉም፣ ታማኞች ናቸው”
መኪና ከነነፍሱ ገብቶ ተበታትኖ የሚወጣበት ሱማሌ ተራ፣ በመኪና ስርቆት “ሥራ” ላይ ለተሰማሩ ሌቦች መናኸሪያ በመሆን አመታትን አሳልፏል፡፡ ዛሬ በከተማዋ ውስጥ የሚካሄዱ የመኪና ዕቃና የመኪና ዝርፍያዎች ማረፊያቸው ሶማሌ ተራ ነው፡፡ በተለይ እንደ አሁኑ ባለ የክረምት ወቅት የመኪና ዕቃ ዝርፍያ ይጧጧፋል፡፡
ህሊና ታየ በያዝነው ሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ መኪናዋ በሌቦች ተፈታትታ ቀፎዋን እንደቀረች ትናገራለች፡፡ በተፈፀመባት ስርቆት አንጀቷ ብግን ቢል ለፖሊስ ጣቢያ አመለከተች፡፡ ሆኖም ብትጠብቅ ብትጠብቅ ጠብ ያለ ነገር የለም፡፡ ቢቸግራት ለመካኒኳ ነገረችውና፣ የተሰረቁትን ዕቃዎች ገዝቶ እንዲገጥምላት ነገረችው፡፡ መካኒኩ ዕቃውን ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን ጠቁሟት ልሞክር ብሎ ደወለ፡፡ ከሶማሌ ተራ ያገኘው ምላሽ ግን “ሴትየዋ ያልተወሰደባትን ነገር ሁሉ ለፖሊስ አስመዝግባለች፡፡ ደግሞ ስትቆይ ዕቃውን አትፈልገውም ብለን ለሌላ ሰው ሸጥነው” የሚል ነበር፡፡ ህሊና እጅግ ተገረመች፡፡ ሌቦቹ ለፖሊስ ማመልከቷን በምን ተዓምር ሊያውቁ እንደቻሉ አሁንም ድረስ እንቆቅልሽ እንደሆነባት ነው፡፡ በመጨረሻም ከፍተኛ ገንዘብ በማውጣት አዳዲስ ዕቃዎችን ለመኪናዋ ለመግጠም መገደዷንም ተናግራለች፡፡መኪኖችን ከነነፍሳቸው አቁሞ ለመበለት፣ አሁን አሁን ከሱማሌ ተራ ይልቅ ሎሚ ሜዳ፣ አብነት ፊሊጶስና ሰበታ አካባቢዎች ተመራጭ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ በሱማሌ ተራ ግን ዛሬም የተሰረቁ የመኪና ዕቃዎች የተሰረቁበት መኪና ታርጋ፣ ቀንና ቦታ ተፅፎባቸው በማዳበሪያ ወይንም በፌስታል ተቋጥረው ባለቤቶቻቸውን ይጠባበቃሉ፡፡ በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት የዕቃዎቹ ባለቤቶች ወደ ሶማሌ ተራ እንደሚመጡ ሌቦቹ እርግጠኞች ናቸው፡፡ ሱማሌ ተራ ህገወጦች የነገሱባት ግዛት ሆና የምትዘልቀው እስከመቼ ይሆን?

 

Published in ባህል

*ወደ ፖለቲካ የምገባው ህዝብ ማገልገል ስለምፈልግ ነው
*ኢትዮጵያን አርቀንና በረጅም ጊዜ የማናይ ከሆነ፣አባይን መገደብ አያስፈልገንም
*በውጭ ሆነው የሚቃወሙ አገራቸው ላይ መታገል አለባቸው ባይ ነኝ

ከጥቂት ዓመታት በፊት ጠ/ሚኒስትር የመሆን ፍላጐት እንዳለው ገልፆ የነበረው አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ፤ ሰሞኑን ከአሶሼትድ ፕሬስ ጋር ባደረገው ቃለምልለስ “የአገሪቱ ፕሬዚዳንት መሆን እፈልጋለሁ” በማለቱ የመነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ ሆኗል፡፡ በ2007 ዓ.ም በሚደረገው አገራዊ ምርጫ ተወዳድሮ ፓርላማ ለመግባት ያሰበው አትሌቱ፤ ከዚያም የአገሪቱ ፕሬዚዳንት በመሆን ህዝብን ማገልገል እንደሚፈልግ ተናግሯል፡፡ 
አትሌት ኃይሌ፤ ከጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ጋር ባደረገው ቃለምልልስ፤ ለምን ወደ ፖለቲካ ሊገባ እንዳሰበ፣ ፕሬዚዳንት ሆኖ ቢመረጥ ለመስራት ስላቀዳቸው ተግባራትና ተያያዥ ጉዳዮች አውግቷል።
እነሆ:- የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ከአትሌት ኃይሌ ጋር

ሰሞኑን “ፕሬዚዳንት መሆን እፈልጋለሁ”ማለትህን ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ከዘገቡ በኋላ ጉዳዩ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ እንዴት ነው ነገሩ?
እኔ የምልሽ ---- ፕሬዚዳንት እንድሆን ኖሚኔት (አጭታችሁኛል) አድርጋችሁኛል እንዴ? ፕሬዚዳንት የሚመረጠው በገዢው ፓርቲ ኖሚኔት ሲደረግ እና ሁለት ሶስተኛውን የፓርላማና የፌደሬሽን ም/ቤት ይሁንታ ሲያገኝ ነው፡፡ እና ይሄ ነገር ሲደጋገምብኝ ---- እንዴት ነው ተጠይቆልኝ ይሆን እንዴ እላለሁ፡፡
ለአሶሽየትድ ፕሬስ በሰጠኸው ቃለ - ምልልስ ላይ ነው ፕሬዚዳንት መሆን እንደምትፈልግ የተናገርከው---
እኔ በእርግጠኝነት የምነግርሽ በ2007 ዓ.ም ፓርላማ እንደምገባ ነው፡፡ ለዚህም ዝግጅት እያደረግሁ ነው፡፡
የት ነው የምትወዳደረው? እዚህ ነው አርሲ?
ኧረ እዚሁ አዲስ አበባ ነው፡፡ የካ ክፍለከተማ ላይ ነው የምወዳደረው፡፡
ለምርጫ ውድድር የሚጠየቁ መስፈርቶችን እንደምታሟላ አረጋግጠሃል?
በሚገባ! በክ/ከተማው ለመወዳደር ህጉ አምስት አመትና ከዚያ በላይ መኖር አለብሽ ይላል፡፡ እኔ ደግሞ እዚያ ክ/ከተማ ውስጥ 10 ዓመት ኖሬአለሁ፡፡ ምርጫው በሚካሄድበት በ2007 ዓ.ም ደግሞ 12 ዓመት ይሆነኛል ማለት ነው፡፡ እርግጥ በትውልድ ስፍራዬ ሄጄም ብወዳደር እንደማሸንፍ ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡
ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን እንደምትፈልግ ተናግረህ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ወደ ፕሬዚዳንትነቱ ዞረሃል--- የመጀመርያውን እቅድ ለምን ተውከው?
ምን መሰለሽ? በአሁኑ ሰዓት እንኳን እኔ ልጆቼም ሲቪክስ ስለሚማሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ ለመመረጥ ምን መደረግ እንዳለበት ያውቃሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን በጣም ረጅም ጊዜ ይወስዳል፡፡ ፓርቲም ማቋቋም ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ ፕሬዚዳንት ለመሆን ግን ፓርቲም አያስፈልግም፡፡ ገዢው ፓርቲ ካመነበትና ብቁ ሆነሽ ከተገኘሽ መሆን ይቻላል፡፡ እኔ ደግሞ ለዚህች አገር መስራት አለብኝ ብዬ የማምን ሰው ነኝ፡፡ ገና ጠቅላይ ሚኒስትር እስከምሆን እርጅና ሊጫነኝ ይችላል፡፡ በዚህ ምክንያት ነው ወደ ፕሬዚዳንትነት የዞርኩት፡፡ በነገራችን ላይ ለዚህች አገር ሥራ ለመስራት ጠቅላይ ሚኒስትርም ፕሬዚዳንትም ሆኖ መመረጥ ላያስፈልግ ይችላል፡፡
ፕሬዚዳንት ለመሆን መፈለግህን በተመለከተ ከአገር ውስጥ ሚዲያዎች ይልቅ ለውጭ ሚዲያ በቅድሚያ መንገርህ ቅሬታ የፈጠረ ይመስላል፡፡ አንተ ምን ትላለህ?
የሚገርመው ለአሶሼትድ ፕሬስ ጋዜጠኛ ኢንተርቪው የሰጠሁት በጠቅላላ ጉዳዮች ላይ እንጂ በፕሬዚዳንትነት ላይ አይደለም፡፡ ነገር ግን በጭውውት መሃል “ፕሬዚዳንት ብትሆንስ እንዴት ነው?” በሚል ጥያቄ ሲነሳ፣ ከተሳካ ለምን አልሆንም የሚል ምላሽ ሰጥቻለሁ፡፡ ጋዜጠኛው ኢትዮጵያዊ ነበር፡፡ እሱ የላከላቸው ሙሉ ቃለምልልሱን ነው፡፡ እነሱ ፕሬዚዳንት የምትለዋን ሃሳብ መዘዙና ሲያጐሏት የሁሉም መነጋገሪያ ሆነ፡፡ ከዚያም እነ ሲኤንኤን፣ አልጀዚራ፣ ዘ ጋርዲያን፣ ቢቢሲ ትኩረት ሰጥተው ሲዘግቡት፣ “ይሄን ያህል ትኩረት መሳብና ተጽእኖ መፍጠር እችላለሁ እንዴ” በሚል ግርምት ውስጥ ገባሁ፡፡ “ፕሬዚዳንት መሆን ትፈልጋለህ ወይ” ሲሉኝ “አዎ ለምን አልሆንም” አልኳቸው፡፡ እነሱም ከዚህ ተነስተው ነው “ወደፊት ፕሬዚዳንት ይሆናል” ያሉት፡፡ ስለዚህ ፕሬዚዳንት እሆናለሁ ብዬ፣ በዚህ ጉዳይ ላይ አስቤበት ለውጭ ሚዲያ ኢንተርቪው አልሰጠሁም፡፡ በዚህ መልኩ የረዱት ካሉ ግን በጣም አዝናለሁ፡፡
የፕሬዚዳንትነት ጥያቄ ቢቀርብልህ ግን ትቀበላለህ?
አሁን ፕሬዚዳንት መሆን የሚጠላ አለ! (ረጅም ሳቅ)
የሚጠላ ሊኖር ይችላል፡፡ መቼም ሁሉም ይፈልጋል አይባልም፡፡
እኔ ግን የሚጠላ ያለ አይመስለኝም---
ስለዚህ እኔም አልጠላም እያልከኝ ነው?
አዎ! ለምን እጠላለሁ --- ግን ለምን ትገፋፊኛለሽ? እንደምታውቂው ከዚህ በፊት በፖለቲካ ውስጥ የመሳተፍ ከፍተኛ ፍላጐት እንዳለኝና በ2007 እንደምወዳደር ቆርጫለሁ፡፡ እንደነገርኩሽ ለመወዳደር እየተዘጋጀሁ ነው፡፡ ፓርላማ መግባቴ የራሴን ሚና ለመጫወት ያግዘኛል፡፡ አሁን ዋናው ትኩረት የሰጠሁት ፓርላማ መግባት ላይ ነው፡፡
በፖለቲካ ውስጥ የመሳተፍ ፍላጎትህ ከምን የመነጨ ነው?
ምን መሰለሽ --- ብዙ ጊዜ እንደምንሰማውና እንደምናየው ሁሌ እንተቻለን እንነቅፋለን፡፡ እንደዚያ ከምናደርግ ለምን የምንነቅፈውን ነገር ውስጥ ገብተን ተሳትፈን አናየውም? ብዙ ነገሮች በውጭና በውስጥ ሆነን ስናያቸው ይለያያሉ፡፡ መቃወምም ካለብሽ ውስጥ ገብተሽ ነው፡፡ መንቀፍም ካለብሽ እንደዛው፡፡ ውስጥ ሆነሽ ስትቃወሚ፣ ይሄ ልክ አይደለም ስትይ፣ ልክ ነው ያልሽውን አማራጭ ሃሳብ አብረሽ ታቀርቢያለሽ፡፡ እንደው ዝም ብሎ በደፈናው ይሄ ልክ አይደለም ይባላል፡፡ “እሺ አማራጭ አቅርብ” ሲባል የለም፡፡ ይህ አይነት ነገር ትንሽ ያናድደኛል፡፡ ስለዚህ እኔ ፓርላማ ውስጥ ገብቼ በሌላው አለም ስዞር በፖለቲካው ዘርፍ ያገኘሁትን ተሞክሮ ማካፈልና አማራጭ ሃሳቦችን ማቅረብ፣ ህዝብ ማገልገል ስለምፈልግ ነው፡፡ በፖለቲካ የመሳተፍ ፍላጐቴም ከዚህ የመነጨ ነው፡፡
“በሌላም አለም ስዞር” ስትል---በሩጫው ማለትህ ነው አይደል?
አዎ! እኔ ከመቶ በላይ የአለም አገሮችን አይቻለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደኔ አለምን የዞሩ ሰዎች ጥቂት ናቸው፡፡ በተለይ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ ከኢትዮጵያ ወጥቼ ቤልጂየምን ካየሁ በኋላ፣ ኢትዮጵያ እንድትሆን የምመኘው ነገር አለ፡፡ ስለዚህ ልምዴን ለኢትዮጵያ ህዝብ ማካፈል አለብኝ፡፡
አንተ እንደልብህ መንቀሳቀስ፣ በነፃነት መሮጥ የለመድክ ሰው ነህ፡፡ ፕሬዚዳንት ሲኮን ግን ነፃነት አይኖርም፡፡ እንቅስቃሴህ ሁሉ በጋርድ የታጀበ ነው የሚሆነው፡፡ እንደፈለጉ መሆን የለም፡፡ የምትችለው ይመስልሃል?
እንዲህ አይነት ነገሮች ሲደጋገሙ ያስቁኛል (ረጅም ሳቅ…) ይህንን ጥያቄ ጓደኞቼም ይጠይቁኛል፡፡ በተደጋጋሚ ማለቴ ነው፡፡ “ከእንግዲህ ጫካ ውስጥ ላናይህ ነው” ይላሉ፡፡ ያው በልምምድ ላይ ማለታቸው ነው፡፡ እኔም “የበለጠ የምንሰራው እንደውም ያን ጊዜ ነው” እላቸዋለሁ፡፡ እርግጥ እዛ ደረጃ ላይ ስትደርሺ ያንን ህግና ስርዓት ማወቅ አለብሽ፡፡ ያ ህግና ሥርዓት ደግሞ ለሀይሌ ብቻ ተብሎ የሚደረግ አይደለም፡፡ ቦታው ስለሚያዝ ነው የሚሆነው፡፡ ቦታው ያዛል ስልሽ ----- ሃይሌ ገ/ስላሴ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ሆኖ የሚደርስበትና እንደ ሃይሌ ገ/ስላሴ እንደራሱ ሆኖ የሚደርስበት ነገር የተለያየ ነው፡፡ እነዚህን ነገሮች የግድ ማወቅ አለብኝ፡፡ የአንድ አገር መሪ ስትሆኚና እንደማንኛውም ሰው ስትሆኚ ይለያያል፡፡
ሰው መሆንና ባለስልጣን መሆን ይለያያል እንደማለት ነው?
አዎ! ለምሳሌ እኔ መሪ ብሆን ከማጣቸው ነገሮች አንዱ ነፃነት የሚባለው ነገር ነው፡፡ እኔ አሁን ሁልጊዜ ግን ሁሉ ነገር እንደሚጠፋ አውቃለሁ፡፡ ስለዚህ ይህን ይህን ሳላስብ ፕሬዚዳንት መሆን እፈልጋለሁ ማለት የማይመስል ነገር ነው፡፡
ሌላው ነገር ፕሬዚዳንትነት የሙሉ ሰዓት ሥራ ነው፡፡ አንተ ደግሞ እጅግ በርካታ ቢዝነሶችን የምታንቀሳቅስ ሰው ነህ፡፡ ይህንንስ እንዴት ታስተናግደዋለህ?
ዋናውና ጠቃሚው ጥያቄ ይሄ ነው፡፡ በድርጅቴ ስር ከአንድ ሺህ በላይ ሰራተኞች ይተዳደራሉ፡፡ እነዚህንም አስቀድሜ ቦታ ማስያዝ አለብኝ፡፡ ቦታ ማስያዝ አለብኝ ስልሽ --- እንደ እኔ ሆኖ ይህን ሃላፊነት ሊሸከም የሚችል ሰው ማዘጋጀት ተገቢ ነው፡፡ እነዚህ እነዚህ ነገሮች ቀድሞ ሊታሰብባቸው እንደሚገባ አይጠፋኝም ማለቴ ነው፡
በእነዚህ ጉዳዮች ላይ አሁን ዝግጁ ነህ?
አሁን ተዘጋጅተሃል ወይ ላልሽው አሁን አልተዘጋጀሁም፡፡ ጊዜ የሚፈልጉ ነገሮች ናቸው፡፡ ስዘጋጅ እነግርሻለሁ፡፡
ፕሬዚዳንት ብትሆን ምን ለውጥ አመጣለሁ ብለህ ታስባለህ? አሁን እንደ ጉድለት የምታያቸውና እሰራቸዋለሁ የምትላቸው ነገሮች ካሉ ብትነግረኝ ----
እኔ እርግጠኛ ሆኜ የምነግርሽ ሥልጣን ባገኝ ብዙ የምሠራቸው ነገሮች እንዳሉ ነው፡፡ ሥልጣኑ የሚኒስትር ይሁን ፕሬዚዳንት በይው--- ምንም በይው ግን በርካታ ስራዎችን እንደምሠራ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ቀላል ልምድ ያካበትኩ አይመስለኝም፡፡ የሰሞኑን የእኔን ዜና ዝም ብለሽ ብታይው ይገርምሻል፡፡ ቅድም እንዳልኩሽ ---- ይህን ያህል ተደማጭና ተጽእኖ ፈጣሪ ነኝ ወይ እስከማለት ደርሻለሁ፡፡ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የእኔን ፕሬዚዳንት የመሆን ፍላጎት በጣም ትኩረት ሰጥተውት ነበር፣ ስለዚህ ይህንን ነገር ተጠቅሜ የራሴን አስተዋጽኦ ማድረግ አለብኝ የሚል ፍላጐት አደረብኝ፡፡ እንደ ዲፕሎማትም በይው እንደምንም ሆኜ ማለቴ ነው፡፡
ቀደም ሲል ለአገር ለመስራት የግድ ፕሬዚዳንትም ጠቅላይ ሚኒስትርም መሆን እንደማያስፈልግ ነግረኸኛል፡፡ ታዲያ የምትፈልገውን ነገር ለመስራት ምን የሚያግድህ ነገር አለ?
እውነት ነው የሚያግደኝ ነገር ላይኖር ይችላል፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ነገሮች እየተለወጡ ነው፡፡ ነገር ግን ውስጥ ሆነሽ ነገሮችን ብትመለከቺና ልምድሽን ብታካፍይ የበለጠ ይህቺን አገር መለወጥ ይቻላል ለማለት ነው፡፡ ለዚህም እርግጠኛ ሆኜና አስረግጬ የምነግርሽ በ2007ዓ.ም በየካ ክ/ከተማ እንደምወዳደርና ፓርላማ ለመግባት እንደምጥር ነው፡፡
ፕሬዚዳንት ብትሆን ምን ምን ሥራዎችን እንደምታከናውን አልነገርከኝም ----
ቅድም እንዳልኩሽ ብዙ ስራዎችን መስራት እንዳለብኝ አስባለሁ፡፡ ለምሳሌ ብዙ በውጭ የሚኖሩ ሰዎች ነገሮች ተስተካክለውላቸው አገራቸው ላይ እንዲኖሩ ማመቻቸት አንድ ሥራ ነው፡፡ መሪ ስትሆኚ የገዢውን ፓርቲ አላማ ነው የምታራምጂው፣ ይሄ ግድ ነው፡፡ የገዢውን ፓርቲ ፕሮግራም ስታራምጂ አብረሽ ተዛማጅ በሆኑ ሥራዎች ላይ ትሳተፊያለሽ፡፡ ግን ፖለቲካውን የማይነኩ ነገር ግን ለዚህች አገር በጣም ጠቃሚ የሆኑ ነገሮች አሉ፡፡ ሁልጊዜ አገር ስትመሪ መመልከት ያለብሽ፣ የዛሬን፣ የነገን ሳይሆን የሩቁንና የወደፊቱን መሆን አለበት፡፡ ኢትዮጵያን አርቀንና በረጅም ጊዜ የማናይ ከሆነ፣ አባይን መገደብ አያስፈልገንም፡፡ ስለዚህ በዚያ ዙሪያ ብዙ ነገሮችን አደርጋለሁ ብዬ አስባለሁ፣ ፓርላማ መግባት አንዱም ጥሩ የሚሆነው ለዚህ ነው፡፡ ፕሬዚዳንት እንኳን ባይኮን ማለት ነው፡፡ ሰሞኑን በፓርላማ ምን ተዓምር እየተሰራ እንደሆነ ለአንቺ አልነግርሽም፡፡ ሌላው በስራ አጥነት፣ በመልካም አስተዳደር፣ በኤክስፖርት ላይ ብዙ መስራት ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያ አሁንም ኤክስፖርት የምታደርገው በጣም ጥቂት ነው፣ እሱን ማሳደግ ላይ መሠራት አለበት፡፡ ጠቃሚ ያልሆኑ ባህሎቻችን ላይም እንዲሁ፡፡ በእኛ አገር ሰርጋችንም ሀዘናችንም ከአንድ ሳምንት በላይ ይወስዳል፣ ሠርግ ጥሩ ነው? አዎ ጥሩ ነው፣ ግን አንድ ሳምንት ሙሉ ሊወስድ አይገባውም፡፡ ይሄ ወደ ኋላ የሚጐትት ነውና መቅረት አለበት፡፡
ወደ ፖለቲካው የመግባት ፍላጐትህን ባለቤትህ ወ/ሮ አለምን ጨምሮ በርካታ ጓደኞችህና ወዳጆችህ ተቃውመውታል ይባላል፡፡ የአንተ ፍላጐት ደግሞ እየበረታ ነው፡፡ እንዴት ልትቋቋማቸው ነው?
ልክ ነው፡፡ ሚስቴም ልጆቼም፣ ዘመድ ወዳጆቼም ሁሉ አልደገፉትም፡፡ ይሄ ግን መጀመሪያም እዚህ ውሳኔዬ ላይ ስደርስ የምጠብቀው ነገር ነው፡፡ ማንም እንደማይደግፈኝ ማለቴ ነው፣ ለምን እንደሆነ ልንግርሽ? ባለቤቴም ቤተሰቦቼም የእነርሱና የእነርሱ ብቻ እንድሆን እንደሚፈልጉ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ነገር ግን አንድ ነገር የማረጋግጥልሽ ከበፊት ጀምሮ ወደ ፖለቲካው መግባት ምኞቴ ነበር፡፡
ቤልጂየምን ካየሁ በኋላ ኢትዮጵያ እንድትሆን የምመኘው ነገር አለ፡፡ ድሮ ድሮ አውሮፓ ሄጄ ስመጣ፣ ኢትዮጵያ እንዲህ አይነት ህንፃ ቢኖራት፣ እንዲህ አይነት መንገድ ቢኖራት፣ የሚል ምኞት ነበረኝ፣ እሱ እየተሳካልኝ ነው፡፡ ለዚህ ነው በማገኘው ገንዘብ ወዲያውኑ እዚህ እየመጣሁ የምሠራው፡፡ ውጭ ወጥቶ የመስራትና የመኖር አጋጣሚው ስለሌለኝ ግን አይደለም፡፡ እንደነገርኩሽ ያልረገጥኩት አገር የለም፡፡ ዜግነት እንስጥህ ያሉኝ በርካታ አገራት አሉ፣ የሰጡኝም አሉ፣ የተቀበልኳቸውም ያልተቀበልኳቸውም አሉ፡፡ እኔ ግን የማረጋግጥልሽ ኢትዮጵያዊ መሆኔን ነው፡፡ ለምን ብትይ --- አማራጭ የለኝም፡፡ ሌላ ምርጫ አላካትትም፡፡ ሰዎች ይህንን ቢረዱልኝ ደስ ይለኛል፡፡ ተደማጭና ተጽእኖ ፈጣሪ ከሆንኩ ሰርቼ ማሳየት አለብኝ፡፡ እኔ አገር ጥሎ መጥፋትን ለሰው ማሳየት አልፈልግም፣ አላደርገውም፡፡
ቤተሰቦቼ ፖለቲካ ውስጥ ለምን ገብተህ ትቸገራለህ ይሉኛል፣ ግን የአቅሜን መስራት አለብኝ እላለሁ፡፡ በውጭ ሆነው የሚቃወሙትም እዚሁ አገራቸው ላይ መታገል አለባቸው ባይ ነኝ፡፡ እንደ ግብጽ፣ እንደ ሶሪያ ባለ መንገድ ዴሞክራሲን ለማምጣት ከውጭ የሚመጣ ካለ እኔም እራሴ እዋጋዋለሁ፡፡ እነ ግብጽ ያተረፉት ነገር የለም፡፡ ችግሮች ካሉ ፓርላማ ገብቶ በሰለጠነ መንገድ መከራከር፣ ችግሮችን ማስተካከል የኢትዮጵያዊያን ሃላፊነት ነው፣ ምክንያቱም ሰላም፣ ጥሩ ኑሮ፣ መልካም አስተዳደር እንዲኖር እንፈልጋለን፡፡ እነዚህ ነገሮች ደግሞ ዝም ብለው እንደ ዳቦ የሚታደሉ አይደሉም፡፡ እነዚህን ነገሮች ለማድረግ ሁላችንም የበኩላችንን አስተዋጽኦ አድርገን፣ ችግሮቻችንን መፍታት መነጋገር እንጂ አገር ጥሎ ሄዶ እሰው አገር ፖለቲከኛ መሆን አያዋጣም፡፡ ለዚህ ነው የቤተሰቦቼን ተቃውሞ ተቋቁሜ ወደ ፖለቲካው የመግባት ፍላጐቴን ያጠነከርኩት፡፡
ሀይሌ አሁን ሩጫ የሚያቆምበት ዘመን ስለሆነ ላለመረሳት ነው ወደ ፖለቲካው ለመግባት ያሰበው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ አንተ ምን ትላለህ?

 

“የትኛውም ፓርቲ ሙስሊሙን ብቻ የሚመለከት ስብሰባ ስለመጥራቱ አላውቅም” ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ፤ የመድረክ አመራር አባልማንኛውም ፓርቲ ሁለት ነገር ተለይቶ መታየት እንዳለበት ነው እማምነው፡፡ አንደኛ ደሴ የተገደሉት የሃይማኖት አባት ጉዳይ የተፈፀመባቸው የነፍስ ግድያ ነው፡፡ ይህም ከፍተኛ የህግ ጥሰት ነው፤ ስለዚህ የእሣቸው ጉዳይ በሃገሪቱ የህግ ስርአት መሰረት፣ ያለሰለሰ ጥረት ተድርጐ ገዳዮቻቸው ለፍትህ መቅረብ አለባቸው፡፡ እኚህ አባት በመሣሪያ ነው የተገደሉት የሚል መረጃ ነው የደረሰን፡፡ ልጆቻቸውም ቤተሰቦቻቸውም በሚዲያ ቀርበው ያረጋገጡት ነገር ነው፡፡ ይህ እንግዲህ የፍትህ ስርአቱ ብቃት የሚታይበት ነው፡፡ የፖለቲካ አጀንዳነቱና ተገቢነቱ ለኔ አይታየኝም፡፡ እኔ መንግስት የእኚህን አዛውንት ሞት በቀላሉ ሳይመለከት ፍትሃዊ እርምጃ መውሰድ አለበት ነው የምለው፡፡ የመንግስትን ወገን በብዙ ነገር መጠርጠር ይቻላል ግን ሁሉም መረጃው ይፋ ከሆነ በኋላ የሚታይ ነው፡፡

“መንግስት የሠራው ድራማ ነው” የሚል ሃሳብ ከሠልፍ አድራጊዎቹም የሰማሁ መሰለኝ፤ ግን መንግስት ገዳዮቹን ይዣለሁ እያለ ነው፡፡ ይህ እንግዲህ በበቂ ማስረጃና በምስክር ነው የሚረጋገጠው፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ሁሉም ሊታወቅ የሚችለው፡፡ “የፖለቲካ ሴራ እየተሰራ ነው፤ የመንግስት ድራማ ነው” የሚለውን ለማመን የሚያስችለኝ ማስረጃ የለኝም፡፡ ይህን የሚሉትን ወገኖች ሃሳብ የምጋራበትም በቂ ምክንያት አይኖረኝም ማለት ነው፡፡ መንግስት የዜጐችን ህገመንግስታዊ መብት እየተጋፋ ነው የሚለው ጉዳይ ለብቻው ነው መታየት ያለበት፡፡ በዚህ ጉዳይ መድረክም ቢሆን “መንግስት ፖለቲካና ሃይማኖትን አጣምሮ ከመንቀሳቀስ እጁን ይሰብስብ፤ ይሄ ኢ-ህገመንግስታዊ ነው” የሚል መግለጫ አውጥተናል፡፡ የተገደሉት የሙስሊም መምህር ስለሆኑ ጉዳዩን ከዚህ ጋር ማገናኘት ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ተቃዋሚዎች የሃይማኖት አጀንዳ ይዘው የተንቀሳቀሱበት ጊዜ ያለ አይመስለኝም፡፡ መብት ይከበር፣ መንግስትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው፣ በሁለቱም ተቋሞች አንዱ በሌላኛው አይገባም የሚል ህገመንግስታዊ ድንጋጌ አለ፡፡

የመንግስት ሚና ምናልባት የሚሆነው በሃይማኖቱ ሰበብ ህግና ስርአቱ ተጥሶ ወንጀል ከተሰራ አንዱ ሌላውን በማጥቃት ላይ ከተሰማራ፣ መቼም የሃይማኖት ተቋማት የራሳቸው ፖሊስ እና ደህንነት የላቸውም፤ ስለዚህ መንግስት ያንን ስርአት የማስያዝ ሃላፊነት ይኖረዋል፡፡ ያ ሃይማኖት ውስጥ ገባ አያስብለውም፡፡ ሆኖም “ይሄን ትመርጣላችሁ፤ ያንን ትጥላላችሁ፤ ይሄን እደግፋለሁ፤ ያንን እቃወማለሁ” ከሚላቸው ነገሮች እጁን መሰብሰብ ይገባዋል፡፡ አንዳንዴ አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎችን ሃሳብ በመደገፍ ጉባኤዎችን እያደረገ፣ ሌሎች በመድረኩ እኩል ተሳታፊ አይሆኑም፡፡ መንግስት ራሱን ከዚህ አውጥቶ ሌሎችንም ያሳምን፡፡ አንዱን ወገን ለይቶ ከሌላው እንደማያስበልጥ በተግባር ያሳይ፡፡ ፓርቲዎችም የሚያነሱትና እያነሱት ያለው ጥያቄ ይሄ ነው፡፡ ከዚህ አልፎ የትኛውም ፓርቲ ሙስሊሙን ማህበረሰብ ብቻ የሚመለከት ስብሰባ፣ ስለመጥራቱ የማውቀው ነገር የለም፡፡ የሙስሊሙ ማህበረሰብ ደግሞ የኢትዮጵያ ዜጋ እንደመሆኑ፣ በአንድ አይነት ህዝባዊ ጥሪዎች ውስጥ እየተገኘ እግረ መንገዱን የራሱን ብሶቶች ቢያሰማ ተገቢ ነው፡፡

በዚህ ደረጃ ነው መታየት ያለበት እንጂ ከዚህ አልፎ ጉዳዮቹን ማጦዝ፣ በየትኛውም አቅጣጫ ቢሆን መግባባት ላይ የሚያደርስ ስለማይሆን፣ መንግስትም ሆነ ተቃዋሚዎች በጥንቃቄ ሊይዙት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ “ኳሱ ያለው በመንግሥት ሜዳ ላይ ነው” ዶ/ር መረራ ጉዲና - የፖለቲካ ሣይንስ ምሁርና የመድረክ አመራር አባል ሃይማኖት የፖለቲካ አጀንዳ መሆኑ በዚህም ሆነ በዚያ ትክክል አይደለም፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን ማነው የጀመረው? ማንስ ነው ወደዚህ ያመጣው? የሚለው ነው፡፡ ለምሣሌ የሙስሊሙ ማህበረሰብ ያን ያህል ችግር ሲደርስበት ተቃዋሚው የኢህአዴግን ጣጣ በመፍራት ዝም ቢል እነሱን እንደዜጐች ያለመቁጠርና ብሶታቸውን ለመስማት ያለመፈለግ ይሆናል፡፡ ተቃዋሚው ተቸግሮ ነው አንዳንድ ነገሮችን ማንሣት የጀመረው፡፡ መንግስት በሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ እየገባ፣ ሰዎች ሲታሰሩና ሲደበደቡ ተቃዋሚው ዝም ቢል ያስወቅሰዋል፡፡ ኢህአዴግ ለምን ወደዚህ ነገር ውስጥ እንደገባ አልገባኝም፤ የሚያሳዝንም ነገር ነው፡፡ ጉዳዩን ለምን ለፖለቲካ ጥቅም ማዋል እንደፈለገ አናውቅም፡፡ ይህን ጨዋታ የጀመረው ምርጫ 97 ላይ ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ደግሞ ለሙስሊሙ ህብረተሰብ ለየት ያለ ፍቅር አለኝ ይል ነበር፤ ከዚያ በኋላ ደግሞ ወደዚህ አይነት ነገር መጥቷል፡፡

መንግስት እንግዲህ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እጁን አስገብቷል፡፡ ለምሣሌ የክርስትና እምነት ተከታዮች በቤተክርስቲያናቸው ጳጳሳቸውን መምረጥ ከቻሉ፣ ሙስሊሞች ለምን በመስጊዳቸው መሪያቸውን መምረጥ አይችሉም፡፡ ይሄ አጠያያቂ ነው፡፡ ይሄኛው በራሱ ቤተክርስቲያን ውስጥ ምርጫ እንዲያካሂድ ከተደረገ፣ እነዚያ ለምን በቀበሌ እንዲያደርጉ ይገደዳሉ፡፡ ይሄ እንግዲህ ኢህአዴግ የለመደውን የቀበሌ ጨዋታ እዚያም ለመድገም የመሞከር ይመስላል፡፡ ዋናው ጉዳይ በእኔ እምነት ኳሱ ያለው በመንግስት ሜዳ ላይ ነው፡፡ መነጋገርም፣ መደራደርም የሚችለው እሱ ነው፡፡ ዝም ብሎ ሁሉንም “ሽብርተኛ” ብሎ መክሰስ አያዋጣም፡፡ ከሱ ቁጥጥር ውጪ የሆኑና መብታቸውን የሚጠይቁትን ሁሉ “ሽብርተኛ” ማለት አይገባም፡፡ ይሄ ነው እንግዲህ ችግር የፈጠረው፡፡ እስካሁን ያለብንን የብሔረሰቦች ጣጣ በአግባቡ ሣንወጣው አሁን ደግሞ ሌላ ጣጣ እያመጣብን ነው፡፡ የሃይማኖት ጉዳይ ቀላል አይደለም፤ እንደሌሎች የፖለቲካ ጥያቄዎችም አይደለም፡፡ እሱን ይዞ ጨዋታ መጀመር ኢህአዴግ ምን እንደሚጠቀምበትም ባናውቅም ውጤቱ ልንወጣው ወደማይቻለን አዘቅት ውስጥ የሚያስገባን ሊሆን ይችላል፡፡ እንደዚህ አይነት ነገሮች ሲፈጠሩ ደግሞ አንዳንዴ ሰው ያላሰበውን ነገርም ማሳሰብ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ በራሱ ላይ የማይሆኑ ቀዳዳዎችንና በሃገሪቱ ላይም ጣጣዎችን ሊያመጣ ይችላል፡፡ ውጤቱ ኢህአዴግ እንደሚለው ቀልድ አይደለም፡፡ “የእኔ ጥያቄ መንግስት በዚህ መጠን ለምን ይጠረጠራል ነው” - አቶ ግርማ ሰይፉ ሰሞኑን ደሴ ውስጥ በተገደሉት የሀይማኖት አባት የተነሳ ሃይማኖትን አጀንዳ አድርጐ እየተንቀሳቀሰ ያለው መንግስት እንጂ ተቃዋሚዎች አይደሉም፡፡

እኛ እየጠየቅን ያለነው መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ አይግባብን፣ ህገ-መንግስቱ ይከበር ነው፡፡ ህገ-መንግስቱ ላይ መንግስትና ሀይማኖት የተለያዩ በመሆናቸው መንግስት ጣልቃ ገብነቱን ያቁም ማለትና የመብት ጥያቄን ማንሳት በምንም መልኩ ሐይማኖትን አጀንዳ አድርጐ መንቀሳቀስ ሊሆን አይችልም፡፡ ስለሆነም እኛ ሃይማኖትን አጀንዳ የማድረግ እቅድም ሃሳብም የለንም፤ በመርህ ደረጃም አንቀበለውም፡፡ የሃይማኖት መሪውን ሞት በተመለከተም መንግስት የፖለቲካ አጀንዳ አድርጐ ለመንቀሳቀስ ቢሞክርም፣ እኔ ግን መንግስትን የሚሠማ ከሆነ ለመምከር የምሞክረው ለምሳሌ እኛ ደሴ ውስጥ ባካሄድነው ሠላማዊ ሰልፍ፣ የደሴ ነዋሪዎች መንግስት እንደሚለው ጥቂት ሳይሆኑ በርካቶች ናቸው፡፡ መንግስት እንደሚለው፤ መቶም ይሁኑ አምስት መቶም ይሁኑ አንድ ሺህ፣ መንግስት በሰውየው ግድያ እጁ አለበት እያሉ እየጠረጠሩ ነው፡፡ መንግስት እጁ አለበት የለበትም የሚለውን ማንም ከእኛ መጠበቅ የለበትም፤ ህዝቡ ራሱ ጥርጣሬ ውስጥ ነው፡፡ ነገር ግን እኛ ማለት የምንፈልገው “መንግስት በዚህ ደረጃ ለምንድነው በህዝብ የሚጠረጠረው ነው” ለምንስ መንግስት በዜጐቹ አይታመንም እያልን ነው ያለነው፡፡ ወደራሱ በጥልቀት መመልከት አለበት የሚል ምክር አለን፡፡ መንግስት “ተቃዋሚዎች ሃይማኖትን አጀንዳ አድርገዋል፤ በእሳት እየተጫወቱ ነው” የሚለው ማስፈራራት ነው፡፡ ማስፈራራት ይቻላል፡፡ እኛ በመርህ ደረጃ ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት፤ ሃይማኖትን አጀንዳ አድርገን አናውቅም፤ ወደፊትም አናደርገውም፤ ህገ-መንግስቱ በሚፈቅደው መሠረት “ሀይማኖታዊ ነፃነት መከበር አለበት” የሚለው መርህ ግን ህገ-መንግስታዊ ነውና በዚህ ዙርያ ባሉት ችግሮች ላይ ሃሳባችንን እናሰማለን፡፡

ይሄ ማለት ግን መንግስት ጣልቃ የሚገባው በእስልምና ሃይማኖት ላይ ብቻ ነው ማለት አይደለም፡፡ በተለያዩ ሃይማኖቶች ጣልቃ ይገባል፡፡ መንግስት ጣልቃ አልገባሁም እያለ ነው፡፡ ግን አልገባሁም ብቻ ሳይሆን “ዜጐች ለምን በዚህ ደረጃ ይጠረጥሩኛል” ብሎ ራሱንም መፈተሽ አለበት። ለምሳሌ ቦስተን ላይ በደረሰው ፍንዳታና ጉዳት የአሜሪካ ህዝብ መንግስትን አልጠረጠረም፤ በቃ የሆነ አሸባሪ አድርጐታል እንጂ መንግስት አድርጐታል ብሎ አልጠረጠረም ታዲያ በእኛ አገር መንግስት ይህን ያህል ለምን በህዝቡ ይጠረጠራል ይህ በጣም ያሳዝናል፡፡ የ“ሃይማኖት ጥያቄ ስህተት የሚሆነው የመንግስትነት ጥያቄ ሲያነሳ ነው” አቶ ሙሼ ሰሙ የኢዴፓ ሊቀመንበር ይህን ነገር ከሁለት አቅጣጫ መመልከት አግባብ ነው፡፡ የመጀመሪያው ከህገመንግስቱና ከህገመንግስቱ ከሚመነጩ መብቶች አኳያ ሊታይ ይገባል፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ከዚሁ ህገመንግስት ቢመነጭም እንደ መብት ለማስተናገድ በሚኖረን ዝንባሌ ላይ መመስረት አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ ደሴ ላይ የተገደሉትን የሃይማኖት አባት በሚመለከት ምንም ጥያቄ የለውም፤ ሰውን በማንኛውም መንገድ ከህግ አግባብ ውጪ መግደል ያስጠይቃል፡፡ በፍርድ ቤት ቀርቦ የሞት ቅጣት እስካልተፈረደበት ድረስ ማንም ሃይል ሰውን የመግደል ስልጣን የለውም፡፡ በዚህ ምክንያት የተፈፀመው ግድያ እጅግ የሚያሳዝንና አግባብነት የሌለው ነው፡፡ ማንኛውም ሰው የሃሳብ፣ የፖለቲካ እና የሃይማኖት ልዩነቱን ማስፈፀም የሚቻለው በህግ አግባብ ሊሆን ይገባል፡፡ የህግ ስርአትን መናድ ከተጀመረ፣ ማብቂያ የሌለው አዙሪት ውስጥ ነው የሚከተን፡፡ ሁለተኛው መንግስት ሌላ ፍረጃ ውስጥ ከመግባቱ በፊት ሊጤኑ የሚገባቸው ነገሮች አሉ ፡- አንደኛ ጉዳዩ በሚገባ መጣራት አለበት፡፡ ይህ መረጃ ለህዝብ ባልደረሰበት ሁኔታ፣ “አሸባሪ ነው፤ የፖለቲካ ጥያቄ ነው፤ የሃይማኖት ጥያቄ ነው” የሚሉ ድምዳሜዎች ላይ ከመድረሱ በፊት አሁንም ጉዳዩን አጥርቶ ማየት ያስፈልጋል፡፡

ይህ ባልሆነበት ከዋናው ስራ በፊት የህዝብ ግንኙነትና የፕሮፓጋንዳ ስራውን ማስቀደም አደጋ አለው፡፡ መንግስት አሁንም አጣርቶ የደረሰበትን መረጃ ግልጽ ያድርግ፣ ህዝቡ የራሱ ጉዳይ ስለሆነ በዚህ ላይ ደግሞ የራሱን አቋም እንዲወስድ ሁኔታውን ያመቻች፡፡ ሁለተኛ ደግሞ በመርህ ደረጃ በህገመንግስቱ መሠረት የፖለቲካ ጥያቄዎች መፍትሔ የሚያገኙት በፖለቲካ መንገድ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የሃይማኖት ጥያቄ ደግሞ ከፖለቲካ ጥያቄዎች ገለልተኛ ጥያቄ ነው፤ ይህ ማለት ግን የፖለቲካ እና የሃይማኖት ጥያቄን የሚያስተሳስራቸው ነገር የለም ማለት አይደለም፡፡ የሃይማኖት ጥያቄ ስህተት የሚሆነው የመንግስትነትን ጥያቄ ሲያነሳ ነው፣ የሃይማኖት ጥያቄው ስልጣንን ለመቆጣጠር የሚደረግ ከሆነ ህገወጥ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ህገመንግስት መሠረት መንግስት ሴኩላር (አለማዊ) ነው፤ ሃይማኖት ውስጥ የማይገባ፣ ሃይማኖትም በመንግስት ጉዳይ የማይገባ ነው፡፡ ስለዚህ የሃይማኖት ጥያቄዎች መስተናገድ ያለባቸው በሃይማኖት አጀንዳ ነው ብዬ አምናለሁ፣ የፖለቲካ ጥያቄዎች ደግሞ በፖለቲካ አጀንዳ ይስተናገዳሉ፡፡ ይህ አጋጣሚ በታሪክ የተፈጠረ ያልታሰበ፣ ያልተጠራ ሂደት ነው ብዬ ነው የምወስደው፡፡ ሙስሊሙ ማህበረሰብ የራሱ ጥያቄ ነበረው፤ ያንን ጥያቄ በተለያየ መንገድ ለመግለጽ በሚፍጨረጨርበት ጊዜ እነዚህ ፓርቲዎች ሠላማዊ ሠልፍ ተፈቅዶላቸው፣ ህጋዊ ሆነው ወጡ፡፡ ያንን አጀንዳ ህብረተሰቡ ከፖለቲካ ጥያቄ ጋር ደርቦ ይዞ ወጣ፤ ይህን ለመቆጣጠር የሚያስችል አሠራር ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት አልነበራትም፡፡

ግን ይሄን እንደ አንድ የታሪክ አጋጣሚ ወስደን፤ ለወደፊት እንዲህ አይነት መደበላለቅ እንዳይፈጠር መስራት ነው የሚያስፈልገው እንጂ ይሄ ነገር ያልተገባ ነው ብሎ ማውገዝ ተገቢ አይደለም፡፡ መንግስት የጉዳዩን አደገኛነት ከግምት ውስጥ አስገብቶ መስመር እንዲያዝ ማድረግ አለበት፡፡ የሙስሊሙ ማህበረሰብ የመብት ጥያቄ አላቸው፤ ያ መድረክ ተመቻችቶላቸው ጥያቄያቸውን የሚያቀርቡበት እድል ማመቻቸት፣ መደበላለቁ እንዳይፈጠር ይረዳል፡፡ ይህ ማለት ግን የሙስሊሞችም ሆነ የሌሎች እምነት ተከታዮች የመብት ጥያቄ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አይመለከታቸውም ማለት አይደለም፡፡ ጥያቄው ከመብት ጥያቄነት ካላለፈ ይመለከታቸዋል፡፡ የመብት ጥያቄን ሌላ ሃይል አይደለም ሊያስተናግድ የሚቻለው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ ሃይል ብቻ ነው፡፡

(ሃተን ሙነቅዮ ዴሬ ኢተ ጋደ ጩቸን መነቅዮ ዴሬ ገከውሱ) - የወላይትኛ ተረት

ከእለታት አንድ ቀን አንድ ዛፍ ቆራጭ ከወንዝ ዳር ዛፍ እየቆረጠ ሳለ መጥረቢያው ከእጁ ወጥቶ፣ ግንዱ ላይ ነጥሮ ወንዙ ውስጥ ወደቀበት፡፡ በወንዙ ዳር ቆሞ፣
“አዬ ጉድ! የእንጀራ ገመዴ ተበጠሰ!” እያለ ሲያለቅስ፤ የውሃው አማልክት መልክተኛ ሜርኩሪ ብቅ አለና፤
“ምን ሆነህ ታለቅሳለህ? ለምን አዘንክ?” አለው፡፡
“የሥራ መጥረቢያዬ ወንዝ ውስጥ ገባብኝ” አለው፡፡
ሜርኩሪ ወደ ውሃው በዋና ጠለቀና አንድ የወርቅ መጥረቢያ ይዞ ወጣ፡፡ ከዚያም፤ “ይሄ መጥረቢያ ያንተ ነውን?” ሲል ጠየቀው፡፡
ዛፍ ቆራጩም፤
“የለም ይሄ የእኔ መጥረቢያ አይደለም” አለና መለሰ፡፡
ሜርኩሪ ለሁለተኛ ጊዜ በዋና ወደ ወንዙ ጠለቀና አንድ ሌላ ከብር የተሰራ መጥረቢያ ይዞ ብቅ አለ፡፡
“ይሄስ ያንተ ነውን?” አለና ጠየቀው፡፡
“እረ የለም ይሄ የእኔ አይደለም” አለ ዛፍ ቆራጩ፡፡
ሜርኩሪ ለሦስተኛ ጊዜ ወደ ውሃው ጠልቆ ሌላ ተራ መጥረቢያ አወጣ
“ይሄስ?” አለው
ዛፍ ቆራጩ “በትክክል ይሄኛው የእኔ መጥረቢያ ነው!” አለ በከፍተኛ ሐሴት ተውጦ፡፡ “እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ!” አለ፡፡
ሜርኩሪም በጣም ረክቶ፤
“ስለታማኝነትህ እነዚህን ሁለት መጥረቢያዎች - ከወርቅ የተሰራውንና ከብር የተሰራውን፤ ሸልሜሃለሁ!” ብሎ ሰጠው፡፡
ዛፍ ቆራጩ ወደ ሰፈሩ ሲደርስ፤
“ዛሬ ትልቅ ፌሽታ ነው ያጋጠመኝ!” ብሎ የሆነውን ሁሉ ለባልንጀሮቹ ነገራቸው፡፡
ከዛፍ ቆራጮቹ አንዱ ቅናት ይይዘዋል፡፡ ስለዚህ ወደ ወንዙ ሄዶ እሱም እድሉን ለመሞር ይወስናል፡፡
ቀናተኛው ዛፍ ቆራጭ አንድ ከወንዙ ዳር ያለ ዛፍ መቁረጥ ይጀምራል፡፡ ከዚያም አውቆ ወደ ውሃው መጥረቢያውን ይወረውረውና፤
“ወይኔ መጥረቢያዬ! ወይኔ የሥራ መሣሪያዬ!” እያለ ይጮሃል፡፡
ይሄኔ ሜርኩሪ ብቅ አለ፡፡
“ምን ሆነህ ነው የምትጮኸው?”
“መጥረቢያዬ በሥራ ላይ ሳለሁ ውሃ ውስጥ ወደቀብኝ” አለ፡፡
ሜርኩሪ ወደ ውሃ ውስጥ ጠለቀና አንድ የወርቅ መጥረቢያ ይዞ ብቅ አለ፤ ከዚያም
“የጠፋብህ መጥረቢያ…” ብሎ ሊጠይቀው ሲጀምር፤
ዛፍ ቆራጩ በስግብግብነት፤
“አዎን፡፡ የኔ የራሴ መጥረቢያ ነው! የገዛ ራሴ መጥረቢያ ነው!!” አለና ሁለት እጆቹን ዘረጋ፡፡
ሜርኩሪ የማይታመን ሰው በመሆኑ በጣም በመከፋት፤
“አንተ ታማኝ አይደለህም! ስለዚህም እንኳንስ፤ የወርቅ መጥረቢያ ውሃ ውስጥ የጣልከውን የራስህን ተራ መጥረቢያም፣ አታገኝም!” አለው፡፡
***
ታማኝነት የህይወታችን መሰረት መሆን አለት፡፡ ለሥራ ታማኝ መሆን አለብን፡፡ ለእውቀት ታማኝ መሆን አለብን፡፡ ለፖለቲካ ታማኝ መሆን አለብን፡፡ ለኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴያችን ታማኝ መሆን አለብን፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ ለሀገራችንና ለህዝባችን ታማኝ መሆን አለብን፡፡ በሌሎች ላይ ልናደርገው ያሰብነውን ወይም ያደግነውን በራሳችን ላይ ሲሆን የምንሸሽ፣ አሊያም መመሪያ የምናወጣበት ከሆነ ታማኝነት የጐደለው ድርጊት ነው፡፡ “ሲያቃጥል በማንኪያ፣ ሲበርድ በእጅ” የምንል ከሆነ ታማኝነት የጐደለው ድርጊት ነው፡፡ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” የምንል ከሆነ ታማኝነት የጐደለው ድርጊት ነው፡፡
ጐር ቫይዳል፤ ምቀኝነትን ሲገልፅ፤ “ጓደኛዬ ሲሳካለት፣ አንድ ነገር ከውስጤ ይሞታል/ይቀንሳል” እንዳለው፤ ጓደኛችን የተሻለ አገኘ ብለን ዐይናችን የሚቀላ ከሆነ ታማኝነት የጐደለው መንፈስ ነው፡፡ “ጐረቤታችን ጫጩት ሲያረባ ስናይ፣ እኛ ሸለምጥማጥ ማርባት የምንጀምር” ከሆነ ፍፁም ታማኝነት የጐደለው የምቀኝነት ድርጊት ነው፡፡ ለእድገት የበቃ ባልደረባችን በደስታ ሲጥለቀለቅ ስናይ እንባ የሚተናነቀን ከሆነ ፈርዶብናል ማለት ነው፡፡ የተያይዘን እንለቅ ፍልስፍና የትም አያደርሰንም - እርግማን ነው፡፡ በሌሎች ደስታ ውስጥ የእኛን ደስታ ለማየት መቻል አለብን፡፡ ደስታችንን ለሌሎች እናጋራ፡፡ ራስ ወዳድነትን እንታገል!
“ደስታን ከራሱ ጋር፣ አጥብቆ ያሰረ
ክንፍ - ያላትን ህይወት፣ ትንፋሽ አሳጠረ፡፡
ደስታ እየከነፈች፣ የሳማት ሰው ግና
የዘለዓለም ፀሀይ ይሞቀዋል ገና”፤ እንዳለው ነው ዊልያም ብሌክ፡፡
ደስታችን የአገር ይሁን እንደማለት ነው፡፡ ደስታ የእኔና የእኔ ብቻ ይሁን ብሎ የሙጥኝ አለማለት ነው፡፡ ከአገር ካዝና የወጣ ደስታ የአገር ነውና ለህዝብ እናዳርሰው፡፡ ለራሳችን ሸሽገን አንቀራመተው ማለት ነው፡፡ የጋራ ቤታችንን እናስብ፡፡ በፓርቲ አጥር አንታጠር፡፡ ደፋር - መሀይም ብቻ ሳይሆን፣ ጭምት - ምሁር የሚኖርባትም አገር እናልም! ዕቡይ - ምሁር ብቻ ሳይሆን ያልተማረ - ጨዋ ህዝብ ያላት አገር እናስብ፡፡ ከፓርቲም ውጪ በቤተሰብ፣ በቢሮ፣ በተቋም፣ በንግድ ድርጅት ውስጥ የሚኖር ነፃ ዜጋ አለ ብለን፣ ከሳጥን ውጪ እንመልከት! ቢያንስ ባስበው ያስበኛል ብሎ ግንዛቤ መውሰድ ያባት ነው፡፡ “የእኔ ወንበር እስካልተነካች ድረስ” የሚል እሳቤ ኃላፊነትን ዘንግቶ አጥር ማጠር፣ ረጅም ጊዜ መኖርን ከዘለዓለማዊነት ጋር ማምታታት ነው (Mistaking Longevity for immortality እንደማለት ነው)፡፡ በዚህም እሳቤ ምክንያት ነው መተካካትን ከብወዛ ጋራ አንድ አድርገን (Mistaking Replacement for Reshuffling እንደማለት) የምናየው፡፡ ወደድንም ጠላንም ቢያንስ ማንም ሰው ሊተካ የሚችል ነው፤ የማይተካ የለም (No one is indespansable) የሚለውን ሁለንተናዊ መርህ ያለራስ ወዳድነት፤ ያለ ምቀኝነት እንቀበል፡፡ ከአጠቃላይ ነባራዊ እውነታው፤ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር፤ አናመልጥም፡፡ እውነታውን ተቀብሎ መፍትሄውን መሻት ከአላስፈላጊና ከማናመልጥበት ሽሽት ይገላግለናል፡፡ አገርም ለቅቀን እንሽሽ ብንል አይሆንም፡፡ ከራስ የህሊና ቁስል ማምለጥ አይቻልምና፡፡ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ የናዚም ወታደር ይያዛል፤ ተብሏል፡፡ በመሸሽ፣ በመሸሸግና ሌላ አገር በድሎት ከመኖር ጋር ራስን ማስተሳሰር ቢያንስ የዋህነት ነው፡፡ እንኳን በባሌ በቦሌም ምቾት ቅርብ አደለም፡፡ ምቾትና ነፃነትን በሌላ ምድር ማግኘት ቀላል አይደለም፡፡ በሰሜንኛ “ጠላ አገኛለሁ ብለህ ውሃ ረግጠህ አትሂድ” ይባላል፡፡ በወላይትኛ ደግሞ “በውሃ የሚያቦኩበት አገር መጥፎ ነው ብላ፤ በምራቅ የሚያቦኩበት አገር ደረሰች” ማለት ነው፡፡ በማህል አገርኛ “ከድጡ ወደ ማጡ” ብለው ያጠቃልሉት ይሆናል፡፡ ብቻ ከዚህ ይሰውረን!!

 

 

 

Published in ርዕሰ አንቀፅ

ባለፈው ሳምንት በጐንደርና በደሴ ሠላማዊ ሰልፍ ያካሄደው አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ፤ ተመሳሳይ ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ ለማካሄድ ከበርካታ ከተሞች የህዝብ ጥያቄ እንደቀረበለት በመጥቀስ በ16 ከተሞች የተቃውሞ ሰልፉንና ህዝባዊ ስብሰባዎች ለማካሄድ እንደወሰነ ገለፁ፡፡ በአዲስ አበባ ሐምሌ 28 ቀን ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ ታቅዶ እንደነበር የተናገሩት የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊው አቶ ዳንኤል ተፈራ፣ ከጐንደርና ከደሴ የተቃውሞ ሰልፍ ጋር ተመሳሳይ ሰልፍ ለማካሄድ ከተለያዩ የኦሮሚያና የደቡብ አካባቢዎች ተደጋጋሚ የህዝብ ጥያቄ ስለቀረበለት ፓርቲው አዲስ ፕሮግራም ለማውጣት እንደወሰነ ተናግረዋል፡፡ የአዲስ አበባውን ለማዘግየትና መስከረም 5 ቀን 2006 ለማድረግ እንደታሰበ ነግረውናል፡፡

በደቡብ በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ በአማራ፣ በቤንሻንጉል፣ በጋምቤላ እና በሀረሪ ክልሎች ተከታታይ ሠላማዊ ሠልፎችና የአደባባይ ስብሰባዎችን ለማካሄድ ፓርቲው ወስኗል ያሉት አቶ ዳንኤል፤ የአዲስ አበባው ሰላማዊ ሰልፍ ወደ መስከረም ተራዝሟል ብለዋል፡፡ ይሁንና ፓርቲው በአዲስ አበባ በቀጣዮቹ ሦስት ሳምንታት የአደባባይ ወይም የአዳራሽ ስብሰባዎችን ይጠራል ተብሏል፡፡ የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ ሐሙስ እለት ተወያይቶ መርሃግብር እንዳዘጋጀ አቶ ዳንኤል ጠቅሰው፤ በ16 ከተሞች ሰላማዊ ሰልፍ ወይም ህዝባዊ ስብሰባ የሚካሄደው ከሐምሌ 28 ጀምሮ ነው ተብሏል፡፡ በጂንካ፣ በአርባ ምንጭና በባህርዳር ሠላማዊ ሰልፍ በሚካሄድበት በዚሁ እለት፣ በወላይታና በመቀሌ የአደባባይ ስብሰባ እንደሚዘጋጅ ተገልጿል፡፡ ነሐሴ 12 ቀን፣ በወሊሶ፣ በናዝሬት፣ በፍቼ እና በባሌ ሠላማዊ ሰልፍ እንደሚካሄድ አቶ ዳንኤል ጠቅሰው፤ ነሐሴ 26 በድሬዳዋ እና በጋምቤላ የአደባባይ ስብሰባ እንዲሁም በአሶሳ ሰላማዊ ሰልፍ ይኖራል ብለዋል፡፡

በአምቦ፣ በሃዋሳ እና በደብረ ማርቆስ ከተሞችም ነሐሴ ውስጥ ህዝባዊ ስብሰባዎች እንደሚዘጋጁ ፓርቲው ገልጿል፡፡ የሠላማዊ ሰልፎቹና የአደባባይ ስብሰባዎቹ ዋና ዋና ትኩረቶች፣ የፀረ ሽብር አዋጁ ይሰረዝ፣ የኑሮ ውድነትና ስራ አጥነት ይቀረፍ፣ የንግዱ ማህበረሰብ ላይ ያለው ጫና ይቃለል፣ የዜጐች መፈናቀል ይቁም የሚሉ ናቸው ብለዋል - አቶ ዳንኤል፡፡ በደሴና በጐንደር ሰልፎች ላይ ህብረተሰቡ የራሱን ችግሮችም በመፈክር መግለፁን አቶ ዳንኤል ጠቅሰው፤ ከሃይማኖት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች መቅረባቸውንም ተናግረዋል፡፡ የፓርቲው የሰላማዊ ሰልፍና የህዝባዊ ስብሰባ ንቅናቄ መስከረም 5 ቀን በአዲስ አበባ በሚካሄደው መርሃ ግብር እንደሚጠናቀቅ ከገለፁ በኋላ ፣ መስከረም 30 በፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ የሚመረጡ አዳዲስ አመራሮች ቀጣይ የፓርቲውን እንቅስቃሴ ይወስናሉ ብለዋል - አቶ ዳንኤል፡፡

Published in ዜና
Page 6 of 13