በታዋቂው አሜሪካዊ ደራሲ ዋላስ ዲ. ዋትልስ የተጻፈው The Science of Getting Rich በጋዜጠኛና ተርጓሚ ኢዮብ ካሣ የብልጽግና ሳይንሳዊ መንገድ በሚል ርዕስ ተተርጉሞ የታተመ ሲሆን በመጪው ሳምንት ገበያ ላይ ይውላል፡፡ ዘመን ተሻጋሪ የብልጽግና መርህ መሆኑ የተመሰከረለት መጽሃፉ፣ በመላው አለም በሚሊዮን ኮፒዎች የተሸጠውን The secret ጨምሮ፣ ለሌሎች ታዋቂ የብልጽግና መፃህፍት መነሻ እንደሆነ ይነገራል፡፡
ዋላስ ዲ. ዋትልስ በዘመናችን የስኬትና የብልጽግና ሊቃውንት ዘንድ በቀዳሚነት የሚጠቀስ ደራሲ ሲሆን በስኬትና በብልጽግና ንድፈሃሳቦችና ተግባራዊ ትምህርቶች ተጽእኖ ፈጣሪ መሆኑ ይነገርለታል፡፡
ጋዜጠኛና ተርጓሚ ኢዮብ ካሣ፣ የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ምክትል ዋና አዘጋጅ ሲሆን ከዚህ ቀደም ተአምራዊ ሃይል እና ታላላቅ ህልሞች የተሰኙ በስኬትና በብልጽግና ላይ ያተኮሩ ሁለት የጋራ ትርጉም መፃህፍትን ለንባብ ከማብቃቱ በተጨማሪ፣ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በሚያወጣቸው የስኬትና የብልጽግና ጽሁፎቹ ይታወቃል፡፡ ፖለቲካ በፈገግታ እና የመፅሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ለልጆች የተሰኙ መፃህፍትንም ለንባብ አብቅቷል፡፡ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ በገበያ ላይ የሚውለው የብልጽግና ሳይንሳዊ መንገድ ፣ 179 ገጾች ያሉት ሲሆን ዋጋው 40 ብር ነው፡፡ በቅርቡም የዓለማችን ባለፀጎች ያልተነገረ የገንዘብ ምስጢር የተሰኘ መፅሃፉ ለህትመት እንደሚበቃ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በሻሸመኔ ከተማ እና አካባቢዋ ኪነጥበባት አፍቃሪዎች የተቋቋመው “ከአድማስ ፊት” የኪነጥበብ ማህበር 43ኛ ወርሃዊ ዝግጅቱን እና የተመሰረበትን አምስተኛ አመት እንደሚያከብር አስታወቀ፡፡ ነገ ከሰዓት በኋላ በከተማዋ ሁለገብ አዳራሽ በማህበሩ አባላት እና የአካባቢው ማህበረሰብ በተጨማሪ አርቲስት ሜሮን ጌትነት እና አርቲስት ዘላለም ኩራባቸው በክብር እንግድነት ይገኛሉ፡፡ በዝግጅቱ የማህበሩን የአምስት ዓመት ጉዞ የሚያሳይ ዘጋቢ ፊልም የሚቀርብ ሲሆን ሽልማት የሚያሰጥ የግጥም ውድድርም ይኖራል፡፡

ነዋሪነቱ በሰሜን አሜሪካ በሆነው ገጣሚ ሳምሶን ይርሳው ጌትነት የተጻፈው ምልክት የተሰኘ የግጥም መድበል የገጣሚው ቤተሰቦችና የጥበብ አፍቃሪዎች በተገኙበት ትናንት በብሄራዊ ቤተ መዛግብት አዳራሽ ተመረቀ፡፡ከዚህ በፊት በአሜሪካ የተመረቀው የግጥም መድበሉ 100 ገጾች ያሉት ሲሆን፣ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑ ግጥሞች ተካተውበታል፡፡ ለገጣሚው የመጀመሪያ ስራው እንደሆነ የተነገረለት መድበሉ በ23 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡

በየዓመቱ አዳዲስ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎቹን የሚያስነብበን ታዋቂው ወጣት ደራሲ ይስማዕከ ወርቁ፣ ዘንድሮም “ክቡር ድንጋይ” የተሰኘ ረጅም ልቦለድ ለንባብ አቀረበ፡፡ ባለ 200 ገፁ መጽሐፍ ለገበያ የቀረበው በ45 ብር ነው፡፡ ደራሲው ከዚህ ቀደም በ100ሺ ቅጂዎች የተቸበቸበለትን ዴርቶጋዳን ጨምሮ ራማቶሐራና ተከርቸም ሌሎች የረዥም ልቦለድ ሥራዎች ለንባብ ያቀረበ ሲሆን፤ በግጥም መድበሎቹም ዝናን ማትረፉ ይታወቃል፡፡

በታዋቂ የካርቱን ኮሚክ መፅሃፍት ላይ በሚገኙ ጀብደኛ ገፀባህርዮች ላይ ተመስርተው በድጋሚ የተሰሩ እና በተከታታይ ክፍሎች ለእይታ የበቁ የሱፕር ሂሮ ፊልሞች የ21ኛው ክፍለዘመን የሆሊውድ ፋሽን መሆናቸውን ዴይሊ ቴሌግራፍ አስታወቀ፡፡ በተወዳጅነት እና በገበያው ስኬታማ እየሆኑ የመጡት የሱፐር ሂሮ ፊልሞች ባለፈው ዓመት በመላው ዓለም 3.8 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያስገኙ ሲሆን ዘገባው ዘንድሮ ገቢያቸው እስከ 4.5 ቢሊዮን ዶላር ሊደርስ እንደሚችል ተገልጿል፡፡ በሆሊውድ ፊልሞች የገበያ ታሪክ ከፍተኛ ገቢ ከተገኘባቸው 10 ፊልሞች ስድስት ያህሉ የሱፕር ሂሮ ፊልሞች መሆናቸው ያላቸውን አዋጭነት ያሳያል ተብሏል፡፡

በሱፕርሂሮ ፊልሞች ታዋቂዎቹ ኩባንያዎች ማርቭል እና ዲሲ ከፍተኛ ፉክክር ውስጥ መግባታቸውን የገለፀው ዘጋርድያን፤ ማርቭል ፒክቸርስ ባለፉት 15 ዓመታት 28 የሱፕር ሂሮ ፊልሞች ሰርቶ 11 ቢሊዮን ዶላር ዲሲ ፒክቸርስ ባለፉት 35 ዓመታት 23 ሰርቶ 4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደሰበሰቡ አመልክቷል፡፡ በቅርቡ ለእይታ ከሚበቁ የሱፐር ሂሮ ፊልሞች መካከል ሰሞኑን የሚመረቀው “ኪክ አስ 2”፤ ከወር በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ለእይታ የሚበቁት “ሪፕድ”፣ “ዘ ዎልቨሪን”፤ በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ደግሞ “300፡ ራይዝ ኦፍ አን ኢምፓዬር”፣ “ሬድ 2”፣ “ሮቦካፕ ሪቡት” ፣ “2 ገንስ” ፣ “ሲን ሲቲ፡ ኤዴም ቱ ኪል ፎር” እና “ቶር ፡ ዘዳርክ ዎርልድ” ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በ2014 ላይ “ኖህ” ፣ “ካፒቴን አሜሪካ፡ ዘ ዊንተር ሶልጀር”፣ “ዘ አሜዚንግ ስፓይደር ማን 2” ፡ “ኒንጃ ተርትልስ”፣ “ትራንስፎርመርስ 4” እና “ኤክስ ሜን” እንዲሁም በ2015 ደግሞ “ዘ አቬንጀርስ 2” እና “አንትማን” የተባሉ የሱፐር ሂሮ ፊልሞች ለእይታ እንደሚበቁ ይጠበቃል፡፡

የአቫታር ፊልም ዲያሬክተር ጀምስ ካሜሮን እና የሚያከፋፍለው ኩባንያ “20 ሴንቸሪ ፎክስ” በኮፒራይት ጥሰት ለአራተኛ ጊዜ መከሰሳቸውን የዲጂታል ስፓይ ዘገባ አስታወቀ፡፡ በፊልሙ ላይ የሚታዩት የሌላ ዓለም ፍጡራን የሆኑ ገፀባህርያት “ከእኔ በተወሰዱ የጥበብ ሥራዎች የተሰሩ ናቸው” ያለው ዊልያም ሮጀር ዲን የተባለ እንግሊዛዊ ሰዓሊ፤ ሰሞኑን ክስ በመመስረት የ50 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፈለው ጠይቋል፡፡ ከሁለት ወራት በፊት አንድ ሌላ አርቲስት ፊልሙ የፈጠራ ሃሳቤን ሰርቋል በሚል ክስ መመስረቱ የተዘገበ ሲሆን ከዓመት በፊትም “ባትስ ኤንድ በተርፍላይስ” ከተባለው መፅሃፌ የአቫታር ፊልም ጭብጥ ተወስዶብኛል ሲል አንድ ደራሲ ከስሶ እንደነበርም ተወስቷል፡፡

ሆኖም የፊልም ዳሬክተሩ ጀምስ ካሜሮን፤ ሰሞኑን ፊልሙን ሙሉ በሙሉ ከራሱ ምናባዊ ሃሳብ አመንጭቶ እንደሰራው የሚገልፅ ባለ 45 ገፅ ሰነድ ይፋ አድርጓል፡፡ በ2009 እ.ኤ.አ ላይ በ237 ሚሊዮን ዶላር በጀት ተሰርቶ በመላው ዓለም ከ2.8 ቢሊዮን ዶላር በላይ ያስገባው አቫታር፤ በገቢው ከፍተኛነት የምንግዜም ፊልሞች የገቢ ደረጃን በአንደኛነት እንደሚመራ ይታወቃል፡፡ ዲያሬክተሩ ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ፤ ከእንግዲህ ስራው የአቫታር ተከታታይ ክፍል ፊልሞችን መስራት እና ከፊልሙ ጋር ተያያዥ ንግዶችን ማከናወን እንደሆነ ገልጿል፡፡ ባለፉት 10 ዓመታት ከአቫታር ፊልም ባሻገር 5 ጥናታዊ ፊልሞችን የሰራው ጀምስ ካሜሮን፤ ቀጣዮቹ ክፍል 2 እና 3 የአቫታር ፊልሞች በአንድ ወጥ ስክሪፕት እንደሚሰሩ የገለፀ ሲሆን አቫታር 2 በ2015 ፤ አቫታር 3 በ2016 እንዲሁም አቫታር 4 በ2017 ለእይታ ለማብቃት እንደሚያስብ ገልጿል፡፡

በቅርቡ “ላይፍ ሃፕንስ” የተባለ አዲስ አልበም በእስራኤል ለገበያ ያበቃችው ቤተእስራኤላዊቷ ድምፃዊት ኤስተር ራዳ፤ በእስራኤል የሙዚቃ ኢንዱስትሪ መድመቅ ጀምራለች ተባለ፡፡ የኤስተር ራዳ አዲስ አልበም አርቲስቷ ኢትዮጵያዊ የዘር ግንዷን ሙሉ ለሙሉ የገለፀችበት ነው ያለው “ኒውስፖይንት አፍሪካ” ፤ “ላይፍ ሃፕንስ” በተባለው ዘፈኗ ዋሽንትና ማሲንቆን እንደተጠቀመች ጠቅሷል፡፡ የ28 አመቷ ድምፃዊት፤ የዘፈን ግጥም ደራሲ እና ተዋናይቷ በአዲሱ አልበሟ ውስጥ “ላይፍ ሃፕንስ” የተሰኘውን የአልበሙን መጠርያ ጨምሮ “ሞንስተርስ”፤ “ኤኒቲንግ ፎር ዩ” እና “ኩድ ኢትቢ” የተባሉ ዘፈኖችን አካትታለች፡፡ በኢትዮ ጃዝ እና በሶል የሙዚቃ ስልቶች የተሰሩት የድምፃዊቷ ዘፈኖች በእስራኤላውያኖቹ እውቅ የሙዚቃ ባለሙያዎች ኩቲ እና ሳቦ የተቀናበሩ እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የኤስተር ቤተሰቦች እ.ኤ.አ በ1983 ዓ.ም በተከሰተው ረሃብ ሳቢያ ኢትዮጵያን ለቅቀው ወደ እስራኤል የተሰደዱ ሲሆኑ ኤስተር የተወለደችው ቤተሰቦቿ እስራኤል ገብተው ኪራያት ኡባ በተባለ ስፍራ መኖር ከጀመሩ ከአንድ አመት በኋላ ነው፡፡ ኤስተር እና ቤተሰቧ 10ኛ ዓመቷን እስክትይዝ ድረስ በሄብሮን ዳርቻ የኖሩ ሲሆን እድሜዋ ለእስራኤል የውትድርና አገልግሎት ሲደርስ ወደ ውትድርናው ገብታ እግረመንገዷን እዚያው በነበረ የሚሊታሪ ባንድ ድምፃዊ በመሆን ሰርታለች፡፡

ቤተእስራዔላዊ ብትሆንም በፀጉረ-ልውጥነቷ ብዙ አሳዛኝ ገጠመኞችን በወጣትነቷ ያሳለፈችው ኤስተር፤የሚሰማትን የመገለል ስሜት በሙዚቃዋ ስትከላከልና ስትዋጋ እንደኖረች አልደበቀችም፡፡ የውትድርና አገልግሎቷን ከጨረሰች በኋላ ኑሯዋን በቴል አቪቭ በማድረግም ወደ ትወና ሙያ እንደገባች ትናገራለች፡፡ በተዋናይነቷ የቴሌቭዥን ፊልሞች የሰራችው ኤስተር፤ ከአራት በላይ የሙሉ ጊዜ ፊልሞች ላይ መተወኗንና “ስቲል ዎኪንግ” እና “ዘ ሩቫቤል” የተባሉት ሁለት ፊልሞች በእስራኤል ፊልም አፍቃሪያን ዘንድ ተወዳጅነት ያተረፉ መሆናቸውን ገልፃለች፡፡

Saturday, 06 July 2013 11:17

“የፍልስምና ፫” መረቦች

ሕይወት የጤዛ ጠብታን ያህል አንሣ የምትታሰበን ጊዜ አለ፡፡ በተለይ ፍልስፍናና ሃይማኖት ውስጥ! ከዚያ ጤዛ ውስጥ ግን ፀሐፍት ዝንታለም የሚኖር ቀለም ያወጣሉ። ያንን ያወጡትን ቀለም በየመልኩ እንደየዘመኑ ያቀጣጥሉታል፡፡ ትውልድ ደግሞ ያንን ምድጃ አቅፎ ይቃጠላል፤ ወይም ይሞቃል…ለዚህ ነው ጠለቅ ያሉ ፍልስፍናዊ ሃሳቦችና ፍልስፍና የተሻሹ፣ ወይም የተቀላቀሉ ግጥሞችም በየጅማቶቻችን ሥር እየነደዱ የሚያነድዱን! ሕያው የሆነ አሳቢን ማለቴ እንጂ ፍሙ ቢጫንባቸው ሕይወታቸውን ሙሉ በድብርት የሚተኙ ሰዎች እንደሚበዙ ዘንግቼው አይደለም! ጥበብ የማንን በር እንደምታንኳኳ ይታወቃል፡፡ ከጭራሮ አጥር ጋር አትቀልድም…ከብረት በር ጋር ትቧቀሳለች እንጂ! ዛሬ የምዳስሰው መጽሐፍ የፍልስፍናውና የሃይማኖቱን ሰፈር ስለሚነካ ነው ልቤ እየዘለለች ጥበብ አጥር ላይ ፊጥ ማለት ያማራት፡፡ ስለጥበብ አናወራም፡፡ ጥበባዊ መዐዛ ስላለው የቴዎድሮስ ተክለአረጋይ መጽሐፍ ግን እኔ ጥቂት እላለሁ። አንባቢዎቼ ደግሞ ያነብቡና እኔንና መጽሐፉን እያመሳከሩ ያነብባሉ፡፡

ቴዎድሮስ “ፍልስፍና 1 እና 2” እያለ የሀገራችንን ሰዎች ፍልስፍናና እምነት በመፈልፈል ወደ 3ኛ አድርሶናል፡፡ ጋዜጠኛና ፀሐፌ ተውኔቱ ቴዎድሮስ በተለያዩ መጽሔቶችና ጋዜጦች ላይ በሚሠራበት ጊዜ አንጀት የሚያርሱ ቃለ ምልልሶችን በድፍረት ስለሚሰራ ብዙዎቻችን በአድናቆት አንገታችንን ነቅንቀንለታል፡፡ ታዲያ እነዚህ መጽሐፍትም በቃለ ምልልስ መልክ የቀረቡ ስለሆነ ሸጋ አድርጐ ይሠራዋል የሚል እምነት ይዘን ያነበብን ይመስለኛል። በእነዚህ መጽሐፍት ውስጥ ትልቁ ነገር አጠያየቁ ቢሆንም ተገቢ ሰዎችን አስሶ ማግኘትም ቀላል ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህንን መሠረት አድርጐም ባሁኑ “ፍልስፍና ፫” - የፍልስፍና መምህርና የቀለም ተመራማሪ፣ የአዕምሮ ሀኪሞች፣ የሥነ ከዋክብት አዋቂ (ወዳጅ) እና ሌሎችን አካትቶ አቅርቧል፡፡ የኔ ትኩረት ግን ወደሰው ልጆች ጥያቄ ቀረብ የሚሉትንና ነፍስን የሚንጡትን ፍልስፍና ጉዳዮች ማየት ነው፡፡ በዚህ ትኩረት ደግሞ አቶ ዜና ላይኩኝ (የእምነት የለሽነት ተከታይ) አቶ ተፈሪ ንጉሤ (የገዳ ሥርዓት ተንታኝ)፣ ቀዳሚዬ ይሆናሉ፡፡

የጌታሁን ሄራሞ (ኬሚካል ኢንጂነር) የቀለም ትንታኔ ጥሞና የሚጠይቅ፣ አዲስና ያልተለመደ ሳይንስ ስለሆነ እርሱን ለብቻ ማጤን የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡ ሌሎቹም ብዙ መልክ አላቸው፡፡ የኔ ቀዳሚ ተመስጦ ግን የገዳ ሥርዓት ተንታኝ ላይ ነው፡፡ ስለገዳ ሥርዓት አቶ ተፈሪ ያነሱት ነገር “ኢትዮጵያዊ በመሆኔ እኮራለሁ” ለሚለው አባባል ትልቅ አቅም የሚጨምር ይመስለኛል። የኦሮሞ ሕዝብ የገዳ ሥርዓት ከግሪክ ሥልጣኔ ዘመን የቀደመ መሆኑን አቶ ተፈሪ መናገራቸው፤ ቴዎድሮስም ይህንን ነገር ጉዳዬ ማለቱ በራሱ ትልቅ ደስታ ይፈጥራል፡፡ ኢትዮጵያውያን የአክሱም ሀውልት፣ የላሊበላና የፋሲል ግንብ ባለቤቶች ብቻ ሳይሆን የዴሞክራሲም ማህፀኖች መሆናችን… አቦ ደስ ይላል! ይህንን ነገር ከጓዳ አውጥቶ በአደባባይ መናገርም በራሱ ታሪክ ነው፡፡

በጣም የሚገርመው ደግሞ አንድ ሰው አባ ገዳ ሆኖ ለመመረጥ የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ ብቻ መሆን የለበትም፤ በባህሉ መሠረት ሌላው ብሔርም በጉዲፈቻና በሌላም መንገድ የብሔሩ አባል ሆኖ ሊመረጥ ይችላል፡፡ (ለመሆን የሚጠበቅበት ጊዜ ግን አለ) አቶ ተፈሪ አንድ ልጅ ወደ አባገዳነት የሚደርስበትን እርከን ሲናገሩ “አንድ ሕፃን እስከ 8 ዓመቱ ድረስ “ኢቲመኮ” ነው የሚባለው፡፡ እነዚህ ሕፃናት ገና እንደተወለዱ በዚያ ዓመት ያለው አባ ገዳ አባላት ነው የሚሆኑት፡፡ ልጆቹ በዚህ ዕድሜያቸው የሚማሩት ዋናው ነገር ማህበራዊ ግንኙነት ነው። ህዝቡን ማወቅ፣ ባህሉንና ቋንቋውንም ማወቅ አለባቸው፡፡ እንዲታወቁ ሊማሩ ግድ ይላል፡፡ ከ9-16 ዓመት እድሜ ያሉት ደግሞ “ደበሌ” ይባላሉ። እነሱ ደግሞ ልምምድ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ልምምዱ ውሃ ዋና፤ ፈረስ ግልቢያ፣ ከብቶች መጠበቅ፣ መላላክ የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ደበሌ ፎሌ፣ ዶሪ የሚባሉትን የዕድሜ እርከኖች ሲያልፉ 40 ዓመት ይሞላቸዋል፡፡ ከዚያ ከ41-48 ያለው የነርሱ አባገዳ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ በሕብረተሰቡ ውስጥ የፍትህ መጓደል ሲከሰት በቀጥታ የሚመለከተው በፎሌ የዕድሜ ክልል ያለውን ነው፡፡ በኦሮሞ ብሔር የውሃ ዋና፣ ተኩስና የመሳሰሉት ሥልጠና የሚወሰድበት ዕድሜ ይህ ነው፡፡ 40 ዓመት ሲሞላው ሕዝብን ለማስተዳደር ይወዳደራል፡፡ ሌላው አስገራሚ ነገር አንድ ሰው ምንም ያህል በሕዝቡ ቢወደድና አስተዳደሩ የተመቸ ቢሆን ከስምንት ዓመት በላይ ሥልጣን ላይ እንዳይቆይ ሥርዓቱ ይከለክላል፡፡ ምርጥ ዴሞክራሲ! የአቶ ተፈሪ ቃለ ምልልስ ስለ ገዳ ሥርዓት ሲያወራ የሴቶችን መብት፣ የሕፃናት ፓርላማ ጉዳይ ሁሉ ያነሳል፡፡

ለገዳ ሥርዓት ይህ አዲስና ብርቅ አይደለም በማለት፡፡ ያ ብቻ አይደለም ስለግሪክ ፍልስፍና ቀዳሚ ያለመሆን ሲናገር እንዲህ ይላል፡- “ሶቅራጥስ ግብጽ መጥቶ ነው የተማረው። ሶቅራጥስ አንድም ነገር አልጻፈም፡፡ ፕሌቶ ነው የጻፈው፡፡ ፕሌቶ ደግሞ አርስቶትልን ያስተምራል። ታሪክ የሚያረጋግጥልን፣ ብዙ ተሸላሚ መጽሐፍት ለምሳሌ ማርቲን ባርናል የፃፈው The Black Atena” መጽሐፍ የሚያሳየን የግሪክ ፍልስፍና የሚባለው የአፍሪካ ፍልስፍና እንደሆነ ነው፡፡ ጆርጅ ጀምስ “The Stolen legacy” የሚለውን መጽሐፍ ጽፎ በአምስተኛው ቀን ተገድሏል፡፡ ያስገደለው የግሪክ ፍልስፍና የግሪክ ሳይሆን የአፍሪካ ፍልስፍና መሆኑን በግልጽ ስላሳየ ነው፡፡ አቶ ተፈሪ ብዙ ጉዳዮችን አንስተዋል፡፡ ከገዳ ጋር በተያያዘ ስለዋቄ ፈና ተንትነዋል፡፡ እኔን ያረካኝና ያስደሰተኝ ጠቅለል ያለው የገዳ ሥርዓት ዴሞክራሲያዊ ውልደትና ውበት በሀገራችን መሆኑ ነው፡፡ ምናልባት በሌሎቹ ነገሮች ወደኋላ እንደተመለስነው በዚህም ወደኋላ ተመልሰናል የሚያሰኝ ይመስለኛል፡፡ ይሁንና በእኒህ ተንታኝ ላይ ያየሁዋቸው ችግሮች አሉ፡፡

አንደኛው “እምነቴ ፕሮቴስታንት ነው” ማለታቸው paradox (አያዎ) ነው፡፡ ምክንያቱም ለምሳሌ ስለሚነትኑት የዋቄፈና እምነት ሲያወሩ ሰይጣን የሚባል ነገር የለም፤ ከሁሉ በላይ የሆነ አምላክ ብቻ ነው እያሉ አጠቃላይ የክርስትናንና ሌሎቹንም እምነቶች በዋቄ ፈና ወገን ሆነው ይናገራሉ፡፡ መልሰው ደግሞ ጓደኞቼ ስለ ክርስቶስ አወሩልኝና ፕሮቴስታንት ሆኜ ነበር ይላሉ፡፡ የሚያምኑት ግን በዋቄፈና ነው፡፡ ስለዚህ የሚጫወቱበትን ሜዳና መለያ ቀይረዋል፡፡ አሁን ያሉበትን እምነት እንጂ ቀድሞ የነበሩበትን መናገራቸው ስህተት ነው፡፡ ለሁሉም እምነትና ፖለቲካ አሁን ያለንበት ነው ተጠቃሽ፡፡ ይሁንና ስለገዳ ሥርዓት በመረጃ በሰጡት ዕውቀት፣ ባጐናፀፉን የማንነት ክብር ተደስቻለሁ፡፡ ስድስተኛ እንግዳ ሆኖ የቀረበው ዜና ለይኩን፤ እግዚአብሔርም ሆነ ሰይጣን የሉም የሚል እምነት አለው፡፡

ቴዎድሮስ ኢ - አማኝነት ከየት መጣ? ሲል ለጠየቀው ጥያቄ ዜና የመለሰው እንዲህ ነው፡- ሃይማኖት ያላቸው ሰዎች ሃይማኖት የሌላቸው ሰዎች ላይ የሚያሳድሩት ጫና ነው ኢ- አማኝነትን የፈጠረው፡፡ ከግሪክ ታሪክ ጀምሮ ብታይ አለማመን ያስገድል ነበር፡፡ ሶቅራጥስን ያስገደለችው አንዲት ትንሽ ጥያቄ ነች፤ አይደል? ግን ትክክለኛ ጥያቄ አልነበረችም፡፡ በዱሮው ዘመን የመጀመሪያው ጥያቄ “እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ ከሆነ፤ ሁሉን አድራጊ ከሆነ ለምን ይህን ያህል ክፉ ነገር በዓለም ላይ ይኖራል?” የሚል ነው፡፡ ይህ የእኔ ብቻ ሳይሆን የማንም አማኝ ጥያቄ መሆን አለበት፡፡ ለእኔማ እግዚአብሔር የለም፡፡ ስለሌለ በዓለም ላይ ክፉ ነገሮች ብዙ አሉ፡፡ በመኖራቸው አዝናለሁ፡፡ ግን የሕይወት መንገድ ነው፡፡” እያለ ነው ዜና የሚቀጥለው፡፡ እዚህ ቃለ ምልልስ ላይ ቴዎድሮስ (ጠያቂው) እና ዜና (ተጠያቂው) በሃሳብ ቡጢ ሁሉ ይገጥማሉ፡፡ ዜና መጽሐፍ ቅዱስን ይጠቅሳል፤ ሌሎች መጻሕፍትንም ጭምር፡፡ ለምሳሌ ቴዎድሮስ “የእግዚአብሔርን መኖር ፋይዳ እና ጥበቡ ሌላ ቢቀር በሥነ ምግባር ትምህርት ቤትነቱ እንኳ አስፈላጊ አይሆንም?” ሲል ይጠይቃል፡፡ ዜና አይሆንም፡፡ ግብረገብን የፈጠረው ሃይማኖት አይደለም፡፡ ከሰብዕና ላይ ነጥቆ የወሰደው ነው፡፡ ቡድሂስቶች ጋ ሂድ፡፡

ከኛ የበለጡ ደጐች ናቸው፡፡ ክርስትና ወይም እስልምና አይደለም ደግ ያደረጋቸው፡፡ ክርስትናን ወይም መጽሐፍ ቅዱስን አያውቁም፡፡ ማንኛውም ሃይማኖተኛ ጥቅምን አስቦ ነው እግዚአብሔርን ያመነው፤ ዘላለማዊ ሕይወትን ለማግኘት፡፡ እኔ ደግ ስሆን ግን ምንም አስቤ አይደለም፡፡ ደግ መሆን ስላለብኝ፤ ሌላ ሰው ደግ ቢሆንልኝ ፋለምፈልግ ነው፡፡ ሁሉንም ሃሳቡን መዘርዘር ባልችልም ዜና ለይኩን መጽሐፉ ውስጥ የተሻለ ምክንያት ይዘው ከተሟገቱት ወይም ከተነተኑት ይመደባል፡፡ ምናልባት የጥያቄው አቅጣጫ ብቻ ይህንን ያደርጋል ማለት አይቻልም፡፡ መልስ የመስጠት አቅሙም የበረታ ነው፡፡ ይሁንና ቀደም ባሉት አንቀፆች ላይ ስለቡድሀ ሃይማኖት ሲጠቀስ፣ እነርሱም አምላክ አለ ብለው ስለሚያምኑ ከእርሱ እምነት ጋር ይጋጫል፡፡ በእርሱ መልስ ከሄድን ክርስትናና እስልምናን ብቻ የሚሞግት ነው፡፡ ይህንን ቴዎድሮስን እንዴት ዝም ብሎ እንዳለፈ አልገባኝም፡፡

አንዳንድ ቦታ ጥሩና ተገቢ ጥያቄዎችን ሲጠይቅ መገኘቱ ነው ቴዎድሮስን የልብ አድራሽ የሚያደርገው፡፡ እዚሁ ዜና ጋ ሌላም ግራ አጋቢ ነገር አለ፡፡ “ደግ እንዲያደርግልኝ ደግ አደርጋለሁ” ይላል፤ ይህ ማለት’ኮ እርሱ ጥቅም ፈልገው ነው እንዳላቸው ሰዎች ጥቅም መፈለጉን ነው የሚያሳየው፡፡ ከዚያም ስለ ቡድሂስቶች ሲናገር “ከኛ የበለጡ ደጐች ናቸው፡፡” በማለት ይገልፃል፡፡ እሱ ማነው?...አማኝ ነው እንዴ? የተጋጨ ሃሳብ ነው፡፡ እንዴት ልብ እንዳላለው አልገባኝም፡፡ እዚህ ጥራዝ ውስጥ በጣም የደነቁኝና የተመቹኝ ያሉትን ያህል ቀለል ያሉብኝና ከዛፍ እንደረገፈ ቅጠል ዝም ብለው የተንኮሻኮሹብኝም አሉ። ለምሳሌ የሥነ ክዋክብቱ ጉዳይ ምንም ስሜት አልሰጠኝም፡፡ ገለባ ሆኖብኛል፡፡

ይህንን ስል ግን ተጋባዡ ዕውቀቱን አላካፈለም እያልኩ አይደለም፡፡ በቂ የሆነ አቅም ያለውና ለቦታው ተመጣጣኝ ሰው ነው፡፡ “ፍልስምና” በሚለው የጥበብ ሰማይ ላይ የዚህ ዓይነት ፈዛዛና ተራ ሃሳቦች ሚዛን ደፊ ናቸው ብዬ አላስብም፡፡ ምናልባት ባለፉት ዓመታት የወጡ የህትመት ውጤቶች ጉዳዩን እያነሱ አሰልችተውን ይሆን? ከፍልስምናም ዘር ጡንቻ ያለው የየዕለቱ ሞጋች ሲሆን ደስ ይላል፡፡ በዘመን ቅደም ተከተል የተሰጡ ሁለት ሃሳቦችም በዚሁ መጽሐፈ የተጋጩ ይመስለኛል፡፡ የዶክተር መስፍንና የኢንጂነር ጌታሁን ሄራሞ ሃሳቦች፡፡ ዶ/ር መስፍን፤ ሕፃን ልጅ ሲወለድ አእምሮው እንደነጭ ወረቀት ነው ሲሉ፣ ኢንጂነር ጌታሁን ሄራሞ ደግሞ የቅርብ ጊዜ መረጃዎችን ጠቅሶ የሰው ልጅ ሲወለድ ከእናቱ ማህፀን የተወሰነ ዕውቀት ይዞ ነው እያለ ይሞግታል፡፡ የአዳማ ዩኒቨርስቲ የፍልስፍና መምህሩ ፈቃዱ ቀነኒሳም በብዙ ዘርፎች ፍልስፍናን ይተነትናል፡፡ ያሁኑ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ መምህር ግን ከቀድሞው መምህር እሸቱ አለማየሁ ጋር ሲተያዩ የዕውቀት ልዩነት የተፈጠረ ይመስላል። መጋቢ ሃዲስ እሸቱ አለማየሁኮ ልበ ብርሃን፣ ጣፋጭና ልዩ ዓይንና አተያይ ያላቸው ብሩና ናቸው። ከሃይማኖቱ ጐራ ተለቅ ያለ ሃሳብ፣ አንፀባርቀዋል፡፡ በጥቅሉ “ፍልስምና ፫ ለእኔ እጅግ በተሻለ ሁኔታ በሳል ሰዎችን የያዘችና አዳዲስ ነገሮችን ያሳየች ናት። አንዳንዴ እየሾለኮ ያመለጡ ሃሳቦችን የቴዎድሮስ መረብ ማስገር ቢሳነውም! ዕውቀትና በሣል ሃሳብ የሚገኘው ታዋቂ ከመሆን ሳይሆን ከአዋቂነት ስለሆነ ጥሩ ጥሩ ሃሳቦች ተነስተዋል ቢባል ማጋነን አይሆንም!

Published in ጥበብ
  • ለትዳር ሽምግልና ሲላክ “አረብ አገር ትልካታለህ ወይ” ተብሎ መጠየቅ ተጀምሯል
  • መምህራን፣ ፖሊሶችና የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች ጭምር እየተሰደዱ ነው

የማህበራዊ ­ጥናት መድረክ ሰሞኑን “የወጣቶች ስደት” በሚል ርዕስ ባዘጋጀው ፕሮግራም ወደ ደቡብ አፍሪካ እና መካከለኛው ምስራቅ የሚደረጉ የስራ ጉዞዎች ላይ ጥናታዊ ፅሁፎች ከመደረጋቸውም በላይ ውይይቶችም ተካሂደዋል፡፡ ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚደረገውን ጉዞ አስመልክቶ ጥናት ያቀረቡት ዶክተር ዘርይሁን በጥናታቸው መግቢያ ላይ፤ ፍልሰት በአገሪቱ ረጅም ታሪክ ያለው እንደሆነ ጠቅሰው፤ የቅርብ ጊዜውን የፍልሰት ታሪክ በሶስት አበይት ክፍሎች በመለየት አስቀምጠዋል፡፡
የመጀመሪያው ዘመን ቅድመ 1966 አብዮት ሲሆን፤ በጣም ውሱን ፍልሰት የታየበት እንደነበርና ይሄ ዘመን ህብረተሰቡ ተምሮ ወደ አገር የመመለስ ሁኔታው የጎላበት ወቅት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ሁለተኛው ከ1966 እስከ 1983 ዓ.ም ያለውን ጊዜ የሚያካልል ሲሆን በአብዛኛው ወደ ምእራቡ አለም የፖለቲካ ስደት የበዛበት፤ ወደ መካከለኛው ምስራቅ የሚደረገውም የስራ ፍልሰት የጀመረበት ወቅት ነበር፡፡ በዚህ ዘመን ፍልሰትን በአሉታዊነት የሚመለከት ፖሊሲ እንደነበረም በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡
ሶስተኛው ድህረ 1983 ሲሆን የመንቀሳቀስ ይሄ ወቅት መብት የተከበረበት፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ስደት እንዲሁም ከፍተኛ የስራ ፍልሰት የታየበት እንደሆነ አጥኚው አመልክተዋል፡፡ ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚደረገው ፍልሰት ከ1990ዎቹ ወዲህ እንደተስፋፋ የጠቆመው ጥናቱ፣ ለዚህም ምክንያቱ በአገር ውስጥ አና በደቡብ አፍሪካ የታዩ ለውጦች እንደሆኑ ተገልጿል፡፡ በአገር ውስጥ ከታየው የመንቀሳቀስና ሰነዶችን በቀላሉ የማግኘት የመብት ለውጥ ባሻገር በደቡብ አፍሪካም የአፓርታይድ ስርአት መውደቅ ያመጣው ምቹ ሁኔታ እንዲሁም በኬኒያ እና በኢትዮጵያ የተደረሰው የቪዛ ስምምነት ተጠቅሰዋል፡፡
ወደ መካከለኛው ምስራቅ የሚደረገውን ፍልሰት ታሪካዊ ዳራ አስመልክቶ ጥናት ያቀረቡት ዶክተር አስናቀ በበኩላቸው፤ ጉዞው ከ1970ዎቹ አንስቶ ቢጀመርም ኢትዮጵያዊያን በብዛት ወደ ሥፍራው መጓዝ የጀመሩት ግን ከ1983 ዓ.ም ወዲህ መሆኑን ጠቅሰው፣ የሴት ተጓዦች ቁጥር በከፍተኛ መጠን በማሻቀብ ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡
በሁለቱም ጥናቶች ላይ የፍልሰቱ ዋነኛ ምክንያት ኢኮኖሚያዊ መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን በመዳረሻ አገሮች ያለው ሰርቶ የማግኘት እድልም ሳቢ ምክንያት እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ለመሄድ የሚገፋፉ ምክንያቶች ተብለው ከተጠቀሱት መካከል፣ በአገር ውስጥ የስራ እድል አለመስፋፋት፣ በተለይ ለገጠር ሴቶች ከግብርና ስራ ውጪ ያሉ የስራ አማራጮች ውሱን መሆንና የጓደኛና የቤተሰብ ተጽእኖ ይገኙበታል፡፡ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ከሚፈልሱት የህብረተሰብ አባላት መካከል በስራ ላይ ያሉ መምህራን፣ ፖሊሶችና የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች ጭምር እንደሚገኙበት ጥናቱ ይጠቁማል፡፡
በጉዞ ወቅት የሚገጥሙ ችግሮችን አስመልክቶ በጥናቱ ላይ እንደቀረበው፣ የደቡብ አፍሪካ ጉዞ በአብዛኛው የሚደረገው በህገወጥ መንገድ በመሆኑ ዋናው ችግር ያለው ደቡብ አፍሪካ እስኪገባ ባለው የጉዞ ሂደት ውስጥ ሲሆን በህጋዊ መንገድ የሚደረገው የመካከለኛው ምስራቅ ጉዞ ችግር የሚጀምረው ደግሞ መዳረሻ አገር ላይ ነው፡፡ ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚደረገው ጉዞ ከአገር ውስጥ እስከ ደቡብ አፍሪካ የተዘረጋ ጠንካራ ኔትወርክ ባላቸው ደላሎች የሚካሄድ ሲሆን በመንገድ ላይ ለሚደርስ እንግልት፣ ስቃይና ሞት ማንም ተጠያቂ አካል እንደሌለ ተጠቁሟል፡፡
የመካከለኛው ምስራቅ ጉዞ ከአገር ከተወጣ በኋላ በህጋዊ መንገድ በሄዱት እና በህጋዊ መንገድ ባልሄዱት መካከል ልዩነት እንደሌለ ያመለከተው ጥናቱ ፤ ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት ወደ ሳኡዲ የሚደረገው ጉዞ በቀጣሪ ኤጀንሲዎች ስምምነት ብቻ የሚከናወን በመሆኑ ተቀጣሪዎች ወደ ተቀባይ አገሮች የሚሄዱትና የሚኖሩት በአሰሪው መልካም ፈቃድ እንደሆነ ይጠቁማል፡፡ ኤጀንሲዎች ህገወጡንና ህጋዊውን ቀላቅለው ይሰራሉ የሚል ጥርጣሬ ማረበቡም ተጠቅሷል፡፡
ፍልሰቱ በአገር ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖዎች እያስከተለ መሆኑ በጥናቱ የተገለፀ ሲሆን ወደ ደቡብ አፍሪካ በሚደረገው ጉዞ በተለይ በደቡብ ክልል ባሉ አካባቢዎች በመንግስት ስራ ላይ ያሉ ሳይቀሩ በመፍለሳቸውና አብዛኞችም ለጉዞው ያኮበኮቡ በመሆናችው የተማረ የሰው ሀይል ላይ የሚያስከትለው መመናመን በአፅንኦት ሊታሰብበት እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡
ፍልሰቱ በተስፋፋባቸው አካባቢዎች ከስደት ይልቅ በአገሩ ሰርቶ መኖር የሚመርጥ ግለሰብ ቢገኝ እንኳን ከህብረተሰቡ ያለበት ጫና ቀላል አለመሆኑን የጠቀሱት አጥኚዎቹ፤ ጎረምሳ ልጅ ያለ ስራ ተቀምጦ ከታየ “ከአንተ የደቡብ አፍሪካ ሬሳ ይሻላል፤ ቢያንስ ሞባይል ይዞ ይመጣል” መባሉን በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ሰው ሞቶ አስከሬኑ ሲላክ ንብረቶቹ አብረው ስለሚላኩ ቢያንስ ሞባይል ከንብረቱ መሀል ስለማይጠፋ እንደሆነ በጥናቱ ተጠቅሷል፡፡
በአማራ ክልል ሴቶች በብዛት ወደ አረብ አገሮች በሄዱባቸው አካባቢዎች ማህበራዊ ለውጦች እየታዩ እንደሆነ የተጠቆመ ሲሆን እናቶች በብዛት በመፍለሳቸው የተነሳ ትንንሽ ሴት ልጆች ላይ ከፍተኛ የስራ ጫና እየተፈጠረ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ልጆቹ በትምህርታቸው እየደከሙ እንደመጡ ታውቋል፡፡
ባሎች ደግሞ ከዚህ በፊት የማይሰሯቸውን የቤት ውስጥ ስራዎች መስራት እንደጀመሩ ጥናቱ ይጠቁማል - ለምሳሌ ወሎ ውስጥ እንደ ሮቢት ባሉ ሴቶች በብዛት ወደ አረብ አገሮች በሄዱባቸው አካባቢዎች፣ ወንዶች የቤት ውስጡን ስራ ሚስቶቻቸውን በመተካት እየሰሩ ይገኛሉ ተብሏል - እንጀራ በመጋገርና ወጥ በመስራት፡፡
በጥናቱ ላይ ከተጠቀሱት ሌሎች ለውጦች መካከልም ህብረተሰቡ ለሴቶች የሚሰጠው ቦታ እየጨመረ መምጣቱ አንዱ ሲሆን የሴቶች ከቤተሰብ ቁጥጥር ውጪ መንቀሳቀስ፣ ሴቶች በተለይ አንደኛ ደረጃን ጨርሰው ትምህርታቸውን ማቋረጥ፣ ዕድሜያቸው 18 ያልሞላ ልጆች ፓስፖርት በማውጣት ፍልሰቱን መቀላቀላቸው እና በሚላከው ገንዘብ የተነሳ በቤተሰብና በትዳር ጓደኛ መሀል ግጭት መፈጠር እንዲሁም በአንዳንድ ቦታዎች ለትዳር ሽምግልና ሲላክ “አረብ አገር ትልካታለህ ወይ” የሚል ጥያቄ መቅረብ መጀመሩ ይጠቀሳሉ፡፡
የጥናት ጽሁፎቹ ከቀረቡ በኋላ በተደረገው ውይይት፤ የሁለት ጎራ ሀሳቦች ከተሳታፊዎች የተሰነዘረ ሲሆን አንደኛው አገር ወስጥ ሰርቶ መለወጥ ይቻላል የሚል ሲሆን ሁለተኛው በአገር ውስጥ መለወጥ ከባድ ነው የሚሉ ናቸው፡፡ መንግስት ለወጣቶች ምቹ እድል መፍጠር አለበት የሚለው ጎልቶ የወጣ ሀሳብ ሲሆን በውይይቱ ላይ ልምዷን ያካፈለች ወጣት ስትናገር፤ “እኔ ውጤት አምጥቼ ዩኒቨርሲቲ ስገባ የጎረቤት ልጆች ውጤት ስላላመጡ ወደ አረብ አገር ሄዱ፤ እኔ ተማሪ ሆኜ እነሱ የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ሕይወት ለውጠዋል፤ እኔ ከተመረቅሁ በኋላ ስራ አላገኘሁም፤ የሚወጣው ማስታወቂያ በሙሉ ከአምስት አመት በላይ የስራ ልምድ ይጠይቃል፤ ሌላ ትምህርት እንዳልማር ወጪ መጋራት በሚለው አሰራር ክፍያ አላጠናቀቅሁም፤ ደቡብ አፍሪካ እህት አለችኝ፤ በየቀኑ እኔም የምወጣበትን መንገድ እንድታመቻችልኝ ነው የምጠይቃት” ብላለች፡፡ እንግዲህ በግልፅ እንደቀረበው ምክንያቱ ምንም ይሁን ምንም ትውልዱ ልቡ ለስደት አሰፍስፏል፡፡ አሳዛኙ ደግሞ ሃይ ባይ ተቆጭ እንኳን አለመኖሩ ነው፡፡ ጎበዝ! ትውልድ ተሰዶ ከማለቁ በፊት ብንወያይበትና መላ ብንዘይድ አይሻልም፡፡

Saturday, 06 July 2013 11:08

የዓመፅ ፍሬ!

ወግ

የመጀመያው አብዮተኛ ሰይጣን ነበር ይባላል፡፡ በዝንተ አለማዊው የእግዚአብሔር አገዛዝ ላይ በተቃውሞ የተነሳ የመላእክት አለቃ፡፡ ይህን አባባል ተቀብለን ለተቃውሞው፣ ለአመፃው ተግባር በመንስኤነት የምናገኘው ሰበብ ቢኖር መሰልቸት ነው፡፡ መሰልቸት ከእጦትም ከቅንጦትም ይመነጫል፡፡ ሊቀ - መልዓኩ በዚያ ፅንፍ አልባ ህዋና በነዚያ ሁሉ እልፍ አእላፍ መላእክት ላይ ሰልጥኖ ሲኖር …ሲኖር አንዳች የሚጐድል፣ አንዳች የሚዛነፍ ነገር የለምና ሰለቸው፡፡ በኛ እምነትም አብዮት ከመለኮት የተገኘ የውርስ ዳፋ ነው፡፡

እንዴት? ቢሉ እልቅናውን የተነጠቀውና ወደ ጥልቁ የተወረወረው ሰይጣን፣ እሱ በተጠመደበት የመሰልቸት ወጥመድ በተራው ሰውን ስላጠመደው፡፡ እንደ ሰይጣን ሁሉ ሰውም (አዳም) በገነት በሙሉ ስልጣን ተሰይሞ ጫፍ እስከ ጫፍ እየተዘዋወረ ያሻውን ይፈጽም ዘንድ ሁሉ በፊቱ ነበር፡፡ ይሄ ፍቃድ በራሱ ለመሰልቸትና ለመተላለፍ በቂ ሆኖ እያለ ሌላ ለሰይጣን ወጥመድ የተመቸ ገደብ ከፈጣሪ ለፍጡሩ ተላለፈ፡፡ “ከህይወት ዛፍ የበላህ እንደሆነ ሞትን ትሞታለህ” የሚል፡፡ ሰይጣን አዳምና ሄዋን በገነት እየተዘዋወሩ እስኪዘሉ፣ እስኪቦርቁ፣ እስኪሰይሙ ታገሳቸው፡፡

የግዜው ርዝመት በራሱ ወደሱ ዓላማ እንዲያመጣቸው ገብቶታል ወደ መሰልቸት፡፡ ግዜው ሲደርስ በጥናቱ መሰረት ተራማጅ ነች ብሎ ወዳመነባት ሄዋን በመሄድ…”አማን ነው ሄዋን”፤ አላት ከወደ ኋላዋ ድንገት ደርሶ “ቆሌህ ይገፈፍ አቦ! ኮቴህም አይሰማም እንዴ!?” አለች እየተበሳጨች አሳቀችው….”እንዴ ኮቴ እኮ የሰው ልጅ ግዴታ ነው፡፡ የኔ መምጣት በምንም ነገር ውስጥ ታምቆ ለመገለጽ አይገደድም” አለ በአካሄዱ እንደመደነስ እየቃጣው፡፡ ለተናገረው ብዙም ትኩረት ሳትሰጥ “እሺ ምን ፈልገህ ነው?” ስትል ጠየቀች፡፡ በተራው ተበሳጭቶ “ወይኔ ሄዋን መፈለግ መመኘት ለናንተ ለስንኩሎቹ የተተወ መባዘን ነው፡፡ እኔ ከዚያ በላይ ያለ ፍቃድ ያለ እግድ የምኖር ነኝ” አላት፡፡ አግድም እያየችው “ማነው ይሄንን ላንተ ብቻ የሰጠው? እኛስ ብንሆን ምን ጐደለብን? እንዳሻን አይደል እንዴ የምንኖረው?” በማስቀናት መልክ ትከሻዋን ነቀነቀች፡፡ “ስቄ ልሞት አለች…እ ትላለች ማለቴ ወደፊት” አለ እየሳቀ፡፡

“እንዳሻን አልሺኝ --- ለዚህ ነዋ ለአዳም ከህይወት ዛፍ ፍሬ የበላህ እንደሆነ ትሞታለህ ብሎ እግዚአብሔር ያስጠነቀቀው!?” ሲል አፋጠጣት፡፡ ሳታስበው ተይዛለችና የምትመልሰው አልነበራትም፡፡ አዳም ከአንበሳ ሲላፋ ትታው የመጣችው የነገሮች ድግግሞሽ አሰልችቷት ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ሰይጣን ከዚህ ሁሉ የበረከት ጋጋታ አንድ ዛፍ መከልከሉን እየነገራት ነው፡፡ “ታዲያ ምን ችግር አለው? በገነት ያለው በረከት በሙሉ በእጃችን ነው-- የአንድ ዛፍ ፍሬ ቢቀርብን ምን እንሆናለን?” ስትል ጠየቀች፡፡

ከመከራከር፣ ከመከላከል ድምፀት ጀርባ ያለውን መሸርሸር፣ ከኋላ ያለውን መዳከም ሰይጣን ነጥሎ አድምጦታል፡፡ “ተይ እንጂ ሄዋን፣ ቢያንስ እኮ ከነዚህ ሁሉ ቁጥር አልባ ዛፎች ተመርጦ የከለከለበት ምክንያት አንድ ልዩ ነገር ቢኖረው ነው፡፡ ተራ ዛፍ አይደለም፡፡ ታዲያ እዚህ ፍሬ ሆድ ውስጥ ያለው ምስጢር እንዴት አያጓጓም ብለሽ ታስቢያለሽ?” ተፈታተናት፡፡ ከሰይጣን ጋር በውይይት በገፋች ቁጥር እየሰላች ከርሱ ጋርም ባልታሰበና ግልጽ ባልሆነ አቅጣጫ እየተስማማች ሄደች፡፡ “በርግጥ ሊያጓጓ ይችላል፤ ግን በውስጡ ያለውን ለማወቅ ከፍሬው መብላት የግድ ነው፡፡ ፍሬውን መብላት ደግሞ ከአምላክ ትዕዛዝ ውጭ መሆን ነው” በስውር አመነታች፡፡

“እሱ እኮ ነው ቁም ነገሩ” አለ ሰይጣን፤ተክለፍልፋ ወደ ወጥመዱ ስትገባለት “የፍሬው ሃይል ገደብ አልባ ያደርግሻል እግዚብሔር በስስት ከአንቺ የጋረደውን አለም ይገልጥልሻል፣ ከአዳዲስ ስሜቶች ጋር ያስተዋውቅሻል፡፡ ፍሬውን ከበላሽ በኋላ አዲስ ምዕራፍ ይከፈታል፣ አሁን የምታውቂውን ያህል የሚሰፋ አለም ላይ ትሰለጥኛለሽ፣ ሌላው ቀርቶ አሁን ባለሽ መረዳት ልትገነዘቢ የማትችይውን በአዳም ላይ ያለሽን የበላይነት ትቀዳጃለሽ” እራሱም በትረካው ተመስጦ ነበር፡፡ “ግን አንተ ይሄን በምን አወቅህ?” በነገሩ በመመሰጧ ስላወቀበት መንገድ እንጂ ስላወቀው ነገር እውነትነት ጥርጣሬው ከውስጧ ጠፍቶ ነበር፡፡ ሳቀ፡፡ ረጅም ሳቅ ሳቀ፡፡ በትንፋሹ ሃይል አዕዋፍ ከዛፍ ሸሽተው እስኪበሩ፣ የየዛፉ ቅጠሎች እስኪረግፉ፣ በግዮን ወንዝ ማዕበል ተነስቶ መስኩን እስኪያጥለቀልቀው፣ ሄዋን ራሷ ቋጥኝ ስር ተደብቃ እስክትንዘፈዘፍ…ሳቀ፡፡ ወዲያው ግን ነቃ ብሎ በኩራት “እንዴ እኔማ ከፈጣሪ መኖር ትንሽ ዘግይቼ ነበርኩ፡፡

ከፈጣሪ እውቀት ትንሽ ብቻ ሲጐድልብኝም ሁሉን አውቃለሁ፡፡ እናም ያንቺና የአዳም ውስንነት ያሳዝነኛል፡፡ ከጽንፍ አልባ አለም ተገድባችሁ ገነት በምትባል ትንሽ መስክ መጣላችሁ ግፍ መሆኑ ይሰማኛል፡፡ ለዚህም ነው ገመድሽን ፍቺ እንዳሻሽ፤ ወዳሻሽ ብረሪ የምልሽ” ይህን ሲናገር መንገድ ጀምሮ ነበር፡፡ አይኗ እሱን ከመከተል ዞር ከማለቱ ከዛፎቹ እንደ አንዱ ሆኖ ይከታተላት ጀመር፡፡ ሃሳብ ሳይሆን መንፈስ የተጋባባት ይመስል እመር ብላ ከተቀመጠችበት ተነስታ አዳምን ትታው ወደመጣችበት አቅጣጫ በትካዜ መሬት መሬቱን እያየች ሄደች፡፡ አዳም እንደተለመደው የተለመደው ተፈጥሮ ብርቅ ሆኖበት በአንክሮ ሲመለከት አገኘችው፡፡ “አዳምዬ?” አለችው እጆቿን ትከሻው ላይ ጣል እያደረገች፡፡

እንዲህ ስትጠራው ልቡ ለምን ድክም እንደሚልበት እየተገረመ “ወዬ ሄዋን” አለ፡፡ የሚሆነው ሁሉ እንደሚሆን እርግጠኛ የሆነው ሰይጣን፡፡ በቅርብ ርቀት ሆኖ በተስፋ ሲቃ የተሞላ ፈገግታው ሁለቱ ፍጡራን ላይ አብርቶ ነበር፡፡ ከሁሉም ጀርባ ሁሉንም በትዝብት የሚመለከተው ፈጣሪ የመከፋቱ ስሜት ዙሪያ ገባውን አደናግዞታል፡፡ አዳምና ሄዋን ብቻ በማይዘልቀው ሰይጣናዊ ብርሃን ስር ሆነው፣ ወደ አዲስ የጨለማ ምዕራፍ እየተሸጋገሩ ነው፡፡

Published in ጥበብ
Page 11 of 13