Saturday, 13 June 2015 15:31

የፍቅር ጥግ

ልክ ነገ እንደሌሌ ያህል አፍቅር፡፡ ነገ ከመጣ ደግሞ እንደገና አፍቅር፡፡
ማክስ ሉሳዶ
መልካም ትዳር የደግነት ውድድር ነው፡፡
ዲያኔ ሳውዬር
ደስተኛ ትዳር ሁልጊዜ አጭር የሚመስል ረዥም ጭውውት ነው፡፡
አንድሬ ማውሮይስ
በጋብቻ ውስጥ ደስታን ማግኘት ሙሉ በሙሉ የዕድል ጉዳይ ነው፡፡
ጄን ኦዩስተን
(Pride & Prejudice)
“ፍቅር”፤ አንድ ሰው መጥቶ ትርጉም እስኪሰጠው ድረስ ተራ ቃል ነው፡፡
ያልታወቀ ደራሲ
አንዱ ጉንጭ ይሰጣል፤ ሌላው ይስማል፡፡ አንዱ ገንዘብ ይሰጣል፤ ሌላው ያጠፋል፡፡
ጆርጅ በርናርድ ሾው
ጋብቻ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ ባለቤታቸውን (ግማሽ ጐናቸውን) እንዲቆጣጠሩ ህጋዊ መብት ለግለሰቦች የሚሰጥ ዓይነት ፈቃድ ነው፡፡
ጄስ ሲ ስኮት
ሁሉም ጋብቻዎች ትዳሮች መንግስተ ሰማያት ነው ይላሉ፡፡ ግን እኮ ነጐድጓድና መብረቅም የሚፈጠሩት እዚያው ነው፡፡
ክሊንት ኢስትውድ
ሰዎች በትዳር የሚዘልቁት ስለፈለጉ እንጂ በሮች ቁልፍ ስለሆኑባቸው አይደለም፡፡
ፖል ኒውማን
ማንም ሴት፤ እናቱን የሚጠላ ወንድ ፈጽሞ ማግባት እንደሌለባት በደንብ አውቃለሁ፡፡
ማርታ ጌልሆርን
ትዳር የተሃድሶ ትምህርት ቤት አይደለም፡፡
ኦን ላንደርስ
ደስተኛ ወንድ የወደዳትን ሴት ያገባል፡፡ የበለጠ  ደስተኛ ወንድ ደግሞ ያገባትን ሴት ይወዳል፡፡
ሱዛን ዳግላስ
የደስታን በሮች የሚከፍተው እናት ቁልፍ ፍቅር ነው፡፡
ኦሊቨር ዌንዴል ሆልሜስ
ትዳር ደስተኛ አያደርግህም፤ አንተ ነህ ትዳርህን ደስተኛ የምታደርገው፡፡
Drs. Les and Leslie Parrott 

Published in ጥበብ


    በዘመናችን በሀሜት ጥርሶች ከሚዘለዘሉት ርዕሰ ጉዳዮች አንዱ የረዥም ልቦለዶች ከንባብ አደባባይ - መጥፋት ነው፡፡ ልብ ሰቃይ ድርሰቶች፣ በምክንያት የተደረደሩ ትርክቶች … አበባ የሰኩ …ዕንባ ያንጠለጠሉ … ሽቱ ያርከፈከፉ … በክፋት የከረፉ ዝንጉርጉር የህይወት ትዕይንቶችን እያሳየ፣ የነፍስን ትርታ የሚያስደንስ የጥበብ ሙዚቃ ለአንባቢዎቹ ናፍቆትና ረሀብ ነው፡፡
የዘመንን መዐዛ የያዘ ንፋስ፣ በፈጠራ ምትሀት ጨብጠው አየሩ ላይ የሚናኙ፣ ባህሉን ፖለቲካውንና ማህበራዊ ክንውኑን ከየዘመኑ ማማ ላይ ቆመው ሥዕሉን የሚያሳዩ ድርሰቶች ርቀት ምሥራቅ ከምዕራብ ያህል ሆኗል ብለው አፍንጫቸውን የሚነፉ አንባቢያንን በየጓዳው ሞልተዋል፡፡
ይሁንና በየጊዜው ደግሞ ይህንን አጥር ጥሰው፣ የዘመኑን ችግር ዘለው ብቅ የሚሉ ደራሲያን አይብዙ እንጂ አሉን፡፡ ከ1950ዎቹ መቋጫ ጀምረው እስከዛሬ ድረስ በየደረጃው ዘመናዊውን የአፃፃፍ መስመርና ልክ ተከትለው በመፃፍ ላይ ናቸው፡፡ ምናልባት በአፃፃፍ ፈንገጥ ያለው የአሁኑ የድህረ ዘመናይነት ተከታይ አዳም ረታ ካልሆነ በስተቀር አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን ደራሲያንና ደራሲያት ከዚህ አጥር ብዙም የራቁ አይደሉም፡፡
ይሄንና በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሚታተሙ መጽሐፍት በአብዛኛው ግለታሪኮችና የህይወት ታሪክ አሊያም በጋዜጦችና በመጽሔቶች የተፃፉ መጣጥፎች መድበል በመሆናቸው የረዥም ልቦለድ ረሀብ የሀገር ሆድ ሲያስጮህ ቆይቷል፡፡
አንዳንዴ ራቅ ብለው ብቅ - ብቅ የሚሉትም አንዳች የጥድፊያና ቴክኒካዊ ብስለት ችግር ይታይባቸዋል የሚለው ሀሜትም ሌላው የንትርክ መነሾ ነው፡፡ ይህንን ስንል ግን ስክን ያለ፣ ሥር ያለው ስራ የሚሰሩ እጅግ እጅግ ጥቂት ደራሲያን የለም ብለን እየካድን አይደለም፡፡ አንዳንዶቹ ተደጋግመው መታተም ሲገባቸው በአንባቢው የንባብና የመረዳት ልክ ተጋርደው ብዙ ሰዎች እጅ ሳይገቡ ቀርተዋል፡፡
መነሻዬ የሀገራችንን ስነጽሑፍ ሚዛን ላይ ማስቀመጥ አሊያም መለካት አይደለም፡፡ ዋና ጉዳዬ ሰሞኑን የታተመው የወይዘሮ ተናኜ ስዩም “የፍቅር ድንግልና” ረጅም ልቦለድ መጸሐፍ ነው። ማለቴ የመጽሐፉን ዳሰሳ በጥቂቱ ማካፈል። መጽሀፉ ከሌሎች ደራሲያን በተለየ እንድናየው የሚያስገድደን አንድ ነገር አለ፡፡ ይኸውም ደራሲዋ እስካሁንም መጽሐፍት ይዘው ብቅ ካሉት ይልቅ በዕድሜ ከፍ ያለች፣ ልጆችና የልጅ ልጆች ያየችም መሆንዋ ነው፡፡ (አንቺ ማለቴ የጥበብን ሰው “አንቱ” ማለት ዝምድናና ቅርበትን መግፋት ስለሚሆን ነው፤ የደራሲ ልብ በየትኛውም ዕድሜ እሸት ነው!) በዚያ ላይ ደግሞ ከቤታቸው ውስጥ ይመጣ የነበረው የጥበብ ምንጭ መነሻም ደራሲዋ ስለሚሆኑ ነው። ከእዚህ ቤት ከያኒዋ እጅጋየሁ ሽባባሁ (ጂጂ) ወጥታለች፡፡ እህቶችዋ ሶፍያ ሽባባው፤ ራሄል ሽባባውና ሌሎችም የጥበብ ሰዎች አሉ፡፡ እንግዲህ ሁሉ ነገር ቀልብ ይስባል፤ ነፍስ ይጋልባል ባይ ነኝ!
በጠና ዕድሜ የተዋጣላቸው የዓለማችን ደራሲያን በቁጥር ጥቂት ይሁኑ እንጂ አሉ። እንደ ጀርመናዊው ገጣሚ፣ ደራሲና የግብርና ባለሙያው ዎልፍ ጋጓግ ዓይነት፡፡ ገተ ተወዳጁን “ዘ-ፎስትን” ያስነበበው 80 ዓመት ካለፈው በኋላ ና፡፡ … ግን ደግሞ ገተ ወንድ ነው፡፡ እንደ ተናኘ ልጆች አያሳድግም። ዘጠኝ ወር አያረግዝም፤ ቤት አያሰናዳም፣ እንጀራ አይጋግርም፤ ልጆች አያጠባም። ተናኜ ግን በዚህ ሁሉ ጣጣ ውስጥ እያለፈች፣ 349 ገፆች ያሉት መጽሐፍ ፅፋለች! … ግርምቱ ከዚህ ይጀምራል፡፡
ያ - ብቻ አይደለም፡፡ ደራሲዋ የተለ ልምድ እንደነበራት ይነገራል፡፡ ገጠር ውስጥ እየኖረች፣ ለድሆች መብት ስትከራከር፣ ሰፈሬውን ሰብሰባ ቴአትር ስታሰራ… እንደኖረች በመጽሐፉ ምረቃ ቀን የተሰጠው እማኝነት ለነፍስ ጮሆ ያወራል። ምናልባትም ሌዎ ኤን ቶልስቶይ ውስጥ የሚታይ ርህራሄና ለድሆች የልብ ቅርብነት እንዳላት ያሳያል። ህይወቱን ከፍሎ፣ ከገበሬው ጋር ተጣብቆ እንደኖረው፣ ገበሬው በተራበ ቀን አዳራሽ አዘጋጅቶ፣ እንጀራ እንደቆረሰው ቶልስቶይ አይነት ልብ አላት ደራሲዋ! ያም ልብ ነው ፍትህን አነፍንፎ፣ ሽንቁር ቀድዶ፣ በብርሃን ዓይን ይህንን ህይወት ያየውና ከታሪክ ጉድጓድ የቀዳው፡፡ የእንባ ዘለላዎች ሲረግፉ በልቧ አጠራቅማ በሌላ አሸንዳ ወረቀት ላይ ሥዕል እንድታስቀምት ያደረጋት! ያ ልብ ነው መንሰፍሰፍና በሰው ህይወት ውቅያኖስ ላይ በሀሳብ መቅዘፍ ያመጣባት፡፡
አረንጓዴ መስክ ላይ ሆኖ ያረረ በረሀ ውስጥ ያሉ ሰዎችን ለማለም ሌላ ዓይን ያስፈልጋል፣ በጠገቡበት አልጋ ተኝቶ፣ የሚቆረቁር መኝታን ማጣጣም ይከብዳል፡፡ …. ግና በፈጠራ ገንዳ ተጠምቆ፣ በፍቅር ዘይት ለታሸ ግን ሁሉ ቅርብ ነው፡፡ ተናኜ እዚህ ውስጥ የምትመደብ ከያኒ ትመስለኛለች፡፡
የተናኜ መሪ ገፀ ባህሪ በአካባቢው ወግ መሰረጽር በጨቅላ ዕድሜዋ ነበር የተዳረችው። ጨዋታ ሳትጠግብ ልጅነቷን ሳትጨርስ ነበር ነጥቀው ለሽፍታ የሰጧት፡፡ እናም የተስፋ አበባ የተመኘች ነፍሷ ሬት ልሳለች፤ በፍቅር የምትነድ ልብዋ በሀዘን ተዳፍናለች። ትዳር ተብሎም እንደ እንስሳ ስትቀጠቀጥ፣ ያለ አሳቢ ተጨብጣ፣ የወሲብ ጥመኞች እርካታ ስትሆን፣ በተቆጨና በነደደ ስሜት ከገፅ ወደ ገፅ እያነበብን ምናልባትም ወንድነታችንን ጠልተንና፣ ተፀይፈን እየገላመጥነው እንድንጓዝ ያደርገናል፡፡ ደግነቱ ግን ደራሲዋ በዚያ ሁሉ የሰቀቀን ወንዝ መሀል ውስጥ ሆና ሁሉም ወንድ እንዲህ ክፉ አይደለም በማለት፣ ከኩነኔው እምብርት፣ ከሲዖሉ አንጀት ውስጥ  ጎትታ ነፃ ታወጣናለች፡፡
ታዲያ ይህ ታሪክ የተዘረዘረበት ቦታ፣ ድርጊቱ የተከወነበት አካባቢ ጎጃም ውስጥ ግንድባ ነው፡፡
ገፀ ባህሪዋ እመቤት፤ አካላዊ ገፅታዋ ገፅ 5 ላይ እንዲህ ይታያል፡- የዓስር ዓመቷ እመቤት ፈጠን እያለች ትራመዳለች፡፡ ያዘለቻት ትንሽ እንስራ ስላልከበደቻች አይደለም፤ እናቷ “ቶሎ ተመለሽ” ብላት እንጂ። የተነገራትን እረስታ ከእኩዮቿ ጋር ስትጫወት ስለቆየች ያንን ለማካካስ ነው የምትጣደፈው፣ ከፈትል የተሰራ ጥብቆ መሳይ ቀሚስ ለብሳለች፡፡ በጋሜዋ መሀል ያለው ቁንጮ ሽሩባዋ በተራመደች ቁጥር ወዲህና ወዲያ ይወዛወዛል፡፡”
ይህቺን ጨቅላ ያገባት ጨካኙና ወንበዴው ደምስ ነው፡፡ ደምስ እንደ ልቡ ነው፡፡ እንደ ሜዳ አራዊት ነው፣ የመታውን መትቶ፣ የገደለውን ገድሎ፣ በሀገሩ ላይ ንጉሥ ሆኖ ይኖራል፡፡ ይፈራል። ያቺ ትንሽ አበባ የገባችው እዚህ አውሬ እጅ ነው። የእመቤት ትኩስ ፍቅር ልብ የተቀመጠው እዚህ የበረዶ ድንጋይ ውስጥ ነው፡፡ ሳቆችዋን የዋጠው ይህ በጭካኔ ጨለማ ውስጥ ያለ አረመኔ ነው፡፡ እንግዲህ ተስፋዋን ካዳፈነው ከዚህ ሰው ጋር ሶስት ዓመት ያህል እንባዋን ስትረጭ ኖራለች፡፡ ከዚያም በኋላ ህይወትዋ የምጥ፣ ኑሮዋ ድጥ ነበር፡፡
ለጥቆ ያገቡዋት ቱጃርም የነፍስዋን ኡኡታ አላረገቡትም፤ የምኞት ክንዶችዋን ሰብረው፣ የራዕይዋን ርቀት አሽመደመዱዋት እንጂ! … የእመቤት ጥቃት ብዙ ነው፡፡ በእመቤት ውስጥ የምናያቸው ኢትዮጵያውያን ሴቶች የደረሰባቸው በደል፣ የተፈፀመባቸው ግፍ - ዝግንን የሚል ነው፡፡
“የፍቅር ድንግልና” ውስጥ እመቤትን ብቻ አይደለም የምናየው፤ ለዚያ ጉስቁልናዋ ምክንያት የሆነውን አስተሳሰብ፣ ባህልና፣ እምነት እንጂ፡፡ በዚያ ዘመን፣ በዚያ ባህል “ሴት ሰው አይደለችም” ተብሎ የሚታመን ይመስላል፡፡ ባይሆንማ ኖሮ እንዴት ህግ ባለበት ሀገር ባንዲራ በሚውለበለብበት አደባባይ፣ አንድ ዜጋ በሀገሯ እንደ በግ እየተነዳች፣ ለወንዶች ወሲብ ስካር ማብረጃ ትሆናለች!? ነፃነት አላት በምትባል ሀገር የምትኖር ዜጋ፣ እንዴት በጨለማ ትኖራለች…?! እንባዋን የሚያይ፣ ሙግትዋን የሚያዳምጥ ህግስ እንዴት አይኖርም? ይህ ብቻ አይደለም፣ “ከፋሽስቱ ጣሊያን እጅ ህዝባችንን ነፃ እናወጣለን” ከሚሉት አርበኞች ሳይቀር የደረሰባት መደፈርና ጥቃት፣ “ምንድነው?” እንድንል ያስገድደን ይሆን?
በአጠቃላይ የእመቤት የህይወት ዘመን ገፅታ የታሪክ ድምፅ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በህይወት ውስጥ የሴት ልብ ጥንካሬ፣ በወንዶች ቢታገዝ ምን ያህል ውጤት እንደሚኖረው የምናይበት ቀዳዳም አለ።
የመጽሀፉን ሙሉ ታሪክ መነካካት የአንባቢን ፍላጎት መዝጋት ስለሆነ ውስጡ ባልገባም መጽሐፉ ውስጥ ብቅ ብቅ ያሉት ሰዎች ሁሉ የየራሳቸው መልክ ያላቸው ናቸው ማለት እችላለሁ፡፡ እንደ አንባቢ ከስሜቴ ውስጥ ስስዋን - መዝዞ ሆዴን ያባባውና አንጀቴን የበላው የእመቤት ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ የጀግናው በላይ ዘለቀ ታሪክ እንደገና ውስጤን ቆስቁሶ፣ ሀዘኔን ጐልጉሎ፣ እንደ እግር እጣት አንገብግቦኛል፡፡ ለሀገር ነፍሱን የሰጠ ጀግና፣ ስለ ሀገሩ ሕይወቱን በሞት ሰይፍ ላይ የነዳ ጐበዝ፣ “ነፃነት ተገኘ” በተባለ ማግስት በገዛ ሀገሩ በሞት መቀጣቱ፣ የኢትዮጵያን የግፍ ግድያ ሚዛን ሰማይ ያስነካዋል፡፡
ደራሲዋ በላይን ስታወራ ከጐኑ ስለ በላይ የተቋጠሩ ስንኞችን፣ የተቀነቀኑ ዜማዎችን አንተርሳለች፡፡
“ሞት” አይቀርም አያ ሥጋ ከለበሱ
ውነት ሙቶ ነወይ የምትላቀሱ፡፡
አባ ኮስትር በሌ ሙተህ ነወይ ለካ
ጀግናው ጀግናው ጐበዝ በአንተ ሳይለካ፡፡
አንቺ የበላይ እናት አንጀትሽን ልቁረጠው
የልጅሽን አንገት ገመድ ቆራረጠው
ድንጋይ ተወርውሮ ዓይኑን አፈረጠው፡፡
እነዚህ ስንኞች ወደ ሦስት አቅጣጫ ያወራሉ፤ ወደ ሕዝቡ፣ ወደ ራሱ ወደ በላይና ወደ እናቱ!
የዚህ ጐበዝ ታሪክ ምናልባት ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያየ መንገድ ሕይወታቸው ካለፈ ጀግኖች ይበልጥ የሚከነክንና የሚቆረቁር ነው፡፡ “ጣሊያን ሠቀለው” ቢባል፣ አንጀቱ ተቃጥሎ ነው፤” እንላለን። ግን የገዛ ሀገሩ ሰቀለችው!...መጽሐፉ ውስጥ አንዱ ከንካኝ ጉዳይ ይህ ነው፡፡ እንደ እኔ እንደ እኔ፣ ያ መቼት ከተነሳ በርግጥም በላይ መቅረት የለበትም። ደራሲዋ ደግ አድርጋለች፡፡
መቼቱን ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ጊዜ ያደረገው ይህ መጽሐፍ፣ በጊዜው በሁለት ቢላ የሚበሉትንም ያሳያል፡፡ ባንድ በኩል አርበኞችን የሚያግዝ፣ በሌላ በኩል ለፈረንጆች የሚያደገድግና ሀብት የሚያጋብስ ነው፡፡ ይህም በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ሁሌ እውነት ነው፡፡
በዚሁ የታሪክ አጋጣሚ ከጣሊያኖች ጋር ቂጥ የገጠመ ባለሥልጣንን ፀሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ሲሞግቱት፤ ሰውየው ልቡን ወደ ሀገሩ ለመመለስ፣ ልጆቹን ለማሳደግ በይፋ መክዳት እንዳለበት ነበር የተናገረው፡፡ ይህ ያኔም ነበር፣ አሁንም ወደፊትም ይኖራል፡፡ ታማኞችም ከሀዲዎችም ሊኖሩ ግድ ነው፡፡ ክርስቶስን እንኳ የከዱትና የሸጡት ሰዎች እንደነበሩ ማስታወስ ከፍ ያለ መረጃ ይሰጣል፡፡
ሌላው በእመቤት ሕይወትና በታሪኩ ውስጥ ጠንካራ ሚና ያላቸው ገፀ ባህሪ አቶ ባለህ ናቸው። እኒህ ሰው ገብስማ ፀጉር፣ አይነ ኮሎ፣ ጥርስ መልካም ናቸው፡፡ ቀልድና ቁምነገር ያውቃሉ። ሁሉንም የሚጠቀሙት ግን ጊዜና ሁኔታዎች ሲመቻቹላቸው ነው፡፡ ስለዚህም የመፍትሔ ሰው ናቸው ብላቸዋለች፤ ደራሲዋ፡፡ ምናልባትም ደራሲዋ በነገረችን እውነት፤ መሥመሩን ሳይለቁ የተጓዙና ስነ ልቡናዊና ማኅበራዊ መልካቸውን በታሪኩ ውስጥ ያስነበቡ፣ በጥንቃቄ የተቀረፁ፣ ገፀ ባህሪ ናቸው፡፡ በጊዜውና ውሣኔ በሚያስፈልግ ሰዐት ደፋር፣ መጠንቀቅ በሚገባ ጊዜ ከሁኔታዎች ጋር የተጣጣመ ውሣኔ ሰጪ ናቸው። ይህንን ደግሞ ከደምስ ጋር በነበረው ድብብቆሽ፣ በኋላም በአቶ ቦጋለ ቤት ድፍረት የተሞላ ውሣኔ አሳይተውናል፡፡
በታሪኩ ውስጥ በምክንያት አንድ መስመር ውስጥ ገብቶ ከእመቤት ሕይወት ጋር የተጋመደው ሙላትና ሙላት የሚረዳቸው የኔ ቢጤ ሴት ወይዘሮ (እማ ዘሬ) ለታሪኩ መፋፋም እንደማራገቢያ ጠቅመውታል፡፡ በተለይ ሙላት የታሪኩ ግንድ ላይ የበቀለ ሌላ ፈርጣማ ግንድ ሆኖ የዋናውን ታሪክ ቁመት ተለካክቶታል፡፡
በብረት አጥር፣ በክልከላ ወሰን የተቀመጠውን የእመቤትና የሙላት የፍቅር ነበልባል አሸንፎ እንዳይወጣ፣ የተጠፈነገበት የምክንያትና የሃይል ገመድ ደራሲዋን አንድ ደራሲ ከሚሾርባቸው ጠንካራ መንስኤና ውጤት ተርታ የሚያስመድብ የጥንካሬ ምስክር ነው፡፡
መጽሐፉ ውስጥ ብዙዎቹ ግጭቶች ምክንያታዊና አሳማኝ ናቸው፡፡ ያ ብቻ አይደለም፣ የታሪኩ ድንኳን ሳይረግብ እየረገጡ የሚያሸጋግሩ በቂ ካስማዎች የተዘጋጁለትም ነው፡፡
የጐጃምን አካባቢ አጠቃላይ አውድ በመጠቀም ቤተክርስቲያን አካባቢ ታሪኩ የሚከርርበትን መንገድ መደልደልዋ በእጅጉ የሚደነቅ ነው፡፡ ምዕራፍ 35 ላይ አዛዥና ሙላትን ለማገናኘት የተቀየሰው ስልት ግሩም የሚባል ነው፡፡
ሌላው ደራሲዋ አንዳንድ ጉዳዮች ተሰውረው ታሪኩን እንዳያደነጋግሩ የምትጠቀምበት መንገድ አንገት የሚያስነቀንቅ ነው፡፡ ለምሳሌ ሙላት ጉም ኢየሱስ ገዳም በሄደ ጊዜ፣ ከእመቤት ጋር ጠበል ቅመሱ ወደተባሉበት ሰው ቤት ሲሄዱ፣ አባትዋ “መንገዱ እንዳይጠፋችሁ” ማለታቸው በኋላ ለሚፈጠረው የእመቤትና የሙላት የናፍቆት ጊዜ ጥሩ የምክንያት ሽንቁር ነው፡፡ ሁለቱ  ሲላፉና ሲጫወቱ፣ ያቺ “መንገዱ ጠፋብን” የምትል ቀብድ ባትኖር ጉድ ይፈላ ነበር!
በአጠቃላይ መጽሐፉ ውስጥ እጅግ በርካታ ውበትና ጥንካሬዎች አሉ፡፡ በተለይ ግጭቶቹ በመንስዔና ውጤት የታጀቡ ናቸው፤ ሴራውም በምቾት የምንፈስስበትና ትንፋሽ እስክናጣ ልባችንን የሚሰቅል ሆኖ የተነደፈ ነው፡፡
በዘመናዊ ሥነ ጽሑፍ ውስጥ ሊካተቱና ሊጠቀሱ የሚገባቸው ነገሮች ሁሉ በመጽሐፉ ውስጥ ጥቅም ላይ ውለዋል ማለት ይቻላል፡፡ ምናልባት ምክንያቱን ባላውቀውም - ደራሲዋ በምልሰት መተረክ ግን አልፈለገችም ወይም ዘንግታዋለች፡፡
ምናልባት አንዳንድ ቦታ ደግሞ የተጐዱትን ለማገዝ፣ የወደቁትን ለመካስ የሚደረግ ነገር ያየሁ ይመስለኛል፡፡ አርስቶትል ወዶ ስለቀደደለት ምን ሊባል እንደሚችል አላውቅም - Poetic justice ይስተዋልበታል፡፡
በጥቅሉ ግን ይህቺ እናት ደራሲ ይህንን በ349 ገፆች የተቀነበበ ረጅም ልቦለድ፤ ልብ በሚያንጠለጥልና አንዳች ረብ ባለው ርዕሰ ጉዳይ አብስላ በመፃፍ ለተደራሲ ማቅረብዋ “አጀብ” የሚያሰኝና በአድናቆት የሚያስጨበጭብ ነው፡፡ ድንቅ ነው ወይዘሮ ተናኜ!  

Published in ጥበብ

  ለደራሲው 10ኛው መጽሐፉ ነው
   “ዴርቶጋዳ” በተሰኘው የመጀመሪያ ልብ ወለድ መፅሃፉ ከፍተኛ ተነባቢነትና ዕውቅናን የተቀዳጀው ወጣቱ ደራሲ ይስማዕከ ወርቁ፤ “ሜሎስ” የተሰኘ አዲስ ልብ ወለድ መጽሐፍ ሰሞኑን ለንባብ ያበቃ ሲሆን 10ኛ መጽሃፉ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡ በ280 ገፆች የተቀነበበውን መጽሐፍ፤የዲዛይንና ህትመት ሥራ ያከናወነው ራሱ ደራሲው ያቋቋመው ዴርቶጋዳ ማተሚያ ድርጅት ነው፡፡ “ሜሎስ” በ60 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡
ይስማዕከ ከዚህ ቀደም “የወንድ ምጥ”፣ “ዴርቶጋዳ”፣ “የቀንድ አውጣ ኑሮ”፣ “ራማቶሓራ”፣ “ተልሚድ”፣ “ተከርቸም”፣ “ዣንቶዣራ”፣ “ክቡር ድንጋይ” እና “ዮራቶራድ” የተባሉ መጽሐፍትን ያሳተመ ሲሆን  አብዛኞቹም በከፍተኛ ቅጂ በመሸጥ ለአሳታሚውም ሆነ ለጸሃፊው ዳጎስ ያለ ገቢ ማስገኘታቸው ይታወቃል፡፡ በተለይ “ዴርቶጋዳ” በጠቅላላው ወደ 200ሺ የሚጠጉ ቅጂዎች በመታተም በኢትዮጵያ የሥነጽሁፍ ህትመት ታሪክ አዲስ ሪከርድ ማስመዝገቡን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ አንዳንድ የሥነጽሁፍ ባለሙያዎችና ሃያሲያን፣ ደራሲው ከመጀመሪያው ሥራው በኋላ ያወጣቸው ተከታታይ  መጻህፍት እያሽቆለቆሉ መምጣታቸውን ቢናገሩም እስካሁን በሥራዎቹ ላይ የሰላ ሂስ የሰነዘረ ወይም ሂሳዊ ጽሁፍ ያቀረበ የለም፡፡

 የመጨረሻ ክፍል
የዲሞክራሲያዊ እና የመሳፍንታዊ ሥርዓት
በተቃራኒው፤ የዲሞክራሲያዊ ማህበረሰብ አባላት አንዱ ከአንደኛው ጋር ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ናቸው። ሆኖም፤ አንዱ ለሌላኛው ሁልጊዜም እንግዳ ነው፡፡ ከእኩልነት ስርዓት መፈጠር ጋር፤ የድሮዎቹ ‹‹ሎሌ›› እና ‹‹ጌታ››ዎች አዲስ ሰውነት ይይዛሉ፡፡ አዲሱ ስርዐት የሁለቱን መደቦች ተነፃፃሪ ማኅበራዊ ቦታ እንዲቀየር አድርጎታል፡፡ ማህበራዊ ምህዳሩ ከሞላ ጎደል የእኩልነት ባህርይ ሲይዝ፤ ሰዎች በኑሮ አውድ ውስጥ የሚይዙት ቦታ ያለማቋረጥ የሚለወጥበት ሁኔታ አለ። በዲሞክራሲያዊ ስርዐት ውስጥ ‹‹የጌቶች›› እና ‹‹የአሽከሮች›› መደብ መኖሩ አልቀረም።  ሆኖም፤ የእነዚህ መደቦች አባላት የሆኑት ሰዎች ሁልጊዜም አንድ ዓይነት ሰዎች ወይም አንድ ዓይነት ቤተሰቦች አይሆኑም፡፡ ይቀያየራሉ። የአዛዥነት ዕድል ያገኙት እና የታዛዥነት ዕጣ የደረሳቸው ሰዎች እንዲያ እንደሆኑ ሊቆዩ አይችሉም። ታዛዡ ሰው፤ ‹‹ታዛዥ እንደሆንኩ ዕድሜዬን እገፋለሁ›› የሚል ስጋት ሊኖረው እንደማይችል ሁሉ፤ አዛዡም፤ ‹‹ያለ አንዳች ስጋት ሁልጊዜም እንዳዘዝኩ እኖራለሁ›› የሚል መተማመን የለውም፡፡ አገልጋዮቹ የተለየ መደብ አይፈጥሩም፡፡ ስለዚህ የተለየ ባህርይ፣ ዝንባሌ ወይም የእነሱ ብቻ መገለጫ የሚሆን አድራጎት አይኖቸውም፡፡ የእነሱ ልዩ መገለጫ ሆኖ የሚጠቀስ የአስተሳሰብ እና የስሜት ዝንባሌ የላቸውም፡፡ ከማህበራዊ አቋማቸው የመነጨ ጥሩ ወይም መጥፎ ምግባር ተብሎ የሚነሳ ነገር የላቸውም፡፡ ይልቅስ፤ የዘመነኞቻቸውን የትምህርት፣ የአስተያየት፣ የስሜት፣ የጥሩ ወይም መጥፎ ምግባር ባህርያትን ይጋራሉ፡፡ ያው ጌታ እንደሚባሉት ሰዎች ሐቀኛ እና ሸፋጮች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
የአሽከሮቹ የኑሮ ሁኔታ ያን ያህል ከጌቶቹ የተለየ አይደለም፡፡ ምክንያቱም፤ በመሳፍንታዊው ስርዐት እንደምንመለከተው፤  በሁለቱ ቡድኖች መካከል የማይለወጥ የደረጃ፣ የማዕረግ ወይም የታዛዥነት መገለጫ የለም፡፡ የትንሽነት ወይም የታላቅነት መገለጫ ባህርይ የሚያሳዩ አይደሉም፡፡ ‹‹በአውሮፓ አሁንም ርዝራዡ ያልጠፋውን የአሽከሮች መደብ ባህርይ እና ድርጊት እንዳስታውስ የሚያደርግ ሰው አሜሪካ ውስጥ አልገጠመኝም›› የሚለው ቶኮቪሌ፤ ‹‹በፈረንሳይ እንዳለው lackey የሚል ቃል በአሜሪካ አልሰማሁም፡፡ የሁለቱ መደቦች መገለጫ የሆኑ ነገሮች ሁሉ ድራሻቸው ጠፍቷል›› ይላል፡፡
በዲሞክራሲ ውስጥ አገልጋዮቹ እርስ በእርስ የሚበላለጡ አይደሉም፡፡ ፍፁም እኩል ናቸው። እኩልነታቸው እርስ በእርስ ብቻ ሳይሆን፤ በሆነ መንገድ ካየነው ከጌቶቻቸውም እኩል ናቸው፡፡ ይህን ሐሳብ በደንብ ለመረዳት ነገሩን ትንሽ አፍታቶ ማየት ይጠይቃል፡፡
አንድ ሎሌ በማናቸውም ጊዜ ጌታ ሊሆን ይችላል። ከእርሱ በላይ ወዳሉት ሰዎች መድረስን ይመኛል፡፡ ስለዚህ አገልጋዩ ከጌታው የተለየ ሰው አይደለም፡፡ ታዲያ ጌታው የማዘዝ መብቱን ያገኘው፤ ሎሌው የታዥነት ግዴታ የተጫነበት በምን ምክንያት ነው? በዲሞክራሲ ስርዐት በነፃ ፈቃድ ከተመሠረተው ጊዜአዊ ስምምነት ሌላ፤ ታዛዡን እና አዛዡን የውል ግዴታ ውስጥ የሚያስገባ ምን ነገር አለ?
በተፈጥሮ አንዱ ከሌላው ያነሰ አይደለም፡፡ አንዱ የሌላው ታዛዥ የሆነው በጊዜያዊ ስምምነት ነው፡፡ ከዚህ የውል ስምምነት በመነጨ ሁኔታ አንዱ አዛዥ ሌላው ታዛዥ ይሆናል፡፡ ከዚህ ውጭ ሁለቱም ሰዎች የአንድ ፖለቲካዊ ህብረት ዜጋ የሆኑ ሁለት ሰዎች ናቸው፡፡ ይህም ነገር በታዛዡም ሆነ በአዛዡ ህሊና ተቀባይነት አግኝቶ ያደረ ጉዳይ ነው፡፡ ታዛዦቹ የሚገኙበትን የኑሮ ሁኔታ የሚመለከቱት ከአዛዡ ሰው በተለየ አይደለም፡፡ የስልጣን እና የታዛዥነቱ ድንበር በግልፅ የተሰመረ እና በሁለቱም ህሊና ውስጥ መልስ አግኝቶ ያደረ ጉዳይ ነው፡፡
የሚበዛው የፖለቲካ ማህበረሰቡ አባላት የኑሮ ሁኔታ ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ሆኖ ውሎ ካደረ  እና እኩልነት በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት አግኝቶ ብዙ በቆየበት ሁኔታ፤ የህዝቡን አስተሳሰብ የሚያዛባ ልዩ ግምት የሚያገኝ ሰው በሌለበት ሁኔታ፤ የሰውን ልጅ ዋጋ የሚወስን አንድ አጠቃላይ ገመታ ይፀናል፡፡ ለአንድ ሰው ከተሰጠው ‹‹ሲቪክ ዋጋ›› በላይ ወይም በታች የሆነ ዋጋ የሚሰጠው ሰው አይኖርም፡፡
በዲሞክራሲ ስርዐት፤  ሐብት እና ድህነት፤ አዛዥነት (ስልጣን) እና ታዛዥነት (ተመሪ) መሆን፤ በመካከላቸው ትልቅ ልዩነት ወይም ርቀት መጋረጡ አይቀርም፡፡ ሆኖም፤ የዘወትራዊ ህይወት ስርዐት ላይ ተደላድሎ የተቀመጠው ህዝባዊ አስተያየት ወይም ህሊና (public opinion)፤ ይህን ልዩነት ጎትቶ ወስዶ በአንድ ሰልፍ ያቆመዋል፡፡ በዚህም በሁለቱ ሰዎች መካከል ያለው ተጨባጭ የኑሮ ሁኔታ ልዩነት እንዳለ ሆኖ፤ ሌላ ሐሳባዊ የእኩልነት መንደር በመፍጠር እኩል አድርጎ ያስተካክላቸዋል፡፡ ይህ ፍፁም ኃያል የሆነ የህዝብ አስተያየት፤ ሌላው ቀርቶ ይህን አመለካከት እንዳይቀበሉና ግድግዳ ሰርተው እንዲከላከሉ የሚያደርግ ጥቅም ካላቸው ሰዎች ልብ ዘልቆ በመግባት፤ መሻታቸውን በማንበርከክ በህሊና ዳኝነታቸው ላይ ተፅዕኖ ያሳርፍበታል፡፡ ስለዚህ፤ ጌታ እና የሎሌዎች፤ ከጥልቅ የልባቸው በኣት ገብቶ ያደረና ሥር ሰድዶ የተቀመጠ ልዩነት በመካከላቸው መኖሩ አይሰማቸውም፡፡
በተለመደ የነገሮች ስርዓት ላይ ተመስርቶ የሚፈጠረው የህዝብ አስተያየት፤ ሁለቱንም ወገኖች ጎትቶ ወስዶ በአንድ ደረጃ ላይ እንዲቆሙ ያደርጋቸዋል፡፡ ተጨባጭ የኑሮ አቋማቸው ውስጥ የሚታየው ተጨባጭ ልዩነት (የበታች እና የበላይ እንዲሆኑ ያደረገው ነገር) እንዳለ ሆኖ፤ በሁለቱ ወገኖች ህሊና ምናባዊ እኩልነት እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡
ይህ ኃያል ጉልበት ያለው አመለካከት፤ ተጨባጩ ጥቅማቸው እኩልነቱን እንዳይቀበሉ ከሚገፋፋቸው ሰዎች ልብ ውስጥ እንኳን ዘልቆ በመግባት፤ የውስጥ ምኞት እና ፍላጎታቸውን አንበርክኮ፤ ለነገሮች በሚሰጡት ዳኝነት ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ በእኩልነት እንዲያምኑ ያደርጋቸዋል፡፡
በጌታ እና በሎሌው ህሊና ጥልቅ የእኩልነት እምነት ተፈጥሯል፡፡ ሁለቱም በመካከላቸው ጥልቅ መሠረት ያለው ልዩነት መኖሩን የሚያምኑ አይደሉም፡፡ በማናቸውም ሰዓት፤ አንዱ አንደኛውን ለመገናኘት በፍርሃት ወይም በተስፋ አይጠብቅም። ስለዚህ፤ አንዱ በሌላው ላይ የቁጣ ወይም የንቀት ስሜት የለውም፡፡ አንዱ ሌላውን በመለማመጥ ወይም በኩራት ስሜት አይቀርበውም፡፡ ‹‹በጌታው›› ዘንድ ያለ ትልቅ ብቸኛው የስልጣን ምንጭ የስራ ስምምነቱ ነው፡፡ በተመሳሳይ፤ ‹‹ሎሌው›› ለቀጣሪው እንዲታዘዝ ምክንያት የሚሆነው ብቸኛ ነገር ይኸው የሥራ ስምምነት ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ጌታው የማዘዝ መብት እንዲያገኝ፤ ሎሌው የመታዘዝ ግዴታ እንዲቀበል የሚያደርግ ነገር የላቸውም፡፡ ሁለቱም ሚናቸውን ያውቁታል፡፡ ከሚናቸው ጋር በተያያዘ ፀብ ውስጥ አይገቡም፡፡ ሁለቱም ወገኖች በየበኩላቸው የሚጠበቅባቸውን ነገር ያውቁታል፡፡ አውቀውም ያከብሩታል፡፡
አሌክሲስ ዲ. ቶኮቪሌ (Alexis de Tocqueville)፤ በምሣሌ የሚያነሳው አንድ ነገር አለ፡፡ በፈረንሳይ መከላከያ ሠራዊት ውስጥ በተራ ወታደርነት የሚቀጠሩት እና በመኮንንነት የሚያገለግሉት ሰዎች ብዙ ጊዜ ከተወሰነ መደብ የሚወጡ ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እናም ከሁለቱም መደቦች የተውጣጡት የሠራዊቱ አባላት፤ በሰራዊቱ የሚሰጣቸው ኃላፊነት ተመሳሳይ ላይሆን ይችላል፡፡ ሆኖም፤ ከወታደራዊ ማዕረጉ ውጭ የበታቹ ከበላዮቹ ጋር ፍፁም እኩል እንደሆነ ያስባል፡፡ በተጨባጭም እኩል ናቸው፡፡ ሆኖም፤ ወታደራዊ ተግባሩን በሚያከናውንበት ጊዜ፤ የበላዮቹን ትዕዛዝ ለመቀበል ፈፅሞ አያመነታም፡፡ ታዛዥነቱ፤ በጎ ፈቃደኝነትን የተጎራበተ፣ ተፈጥሯዊ የመሰለ እና ወትሮ ዝግጁነት ያልተየው ነው፡፡ ይህ ምሳሌ፤ በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ በጌታ እና በሎሌ መካከል ያለው ግንኙነት ምን እንደሚመስል ፍንጭ ሊሰጠን የሚችል ነው፡፡
ሆኖም፤ በመሳፍንታዊ ስርዓት ባሉ ‹‹ጌታ›› እና ‹‹ሎሌ››ዎች መካከል፤ በቤት ውስጥ አገልግሎት አንዳንዴ ሲፈጠር የምናየውን ዓይነት የጋለ እና ጥልቅ የሆነ ፍቅር ወይም መተሳሰብ በዲሞክራሲ ስርዓት ውስጥ በሚኖሩ ጌታ እና ሎሌዎች መካከል ይፈጠራል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡ እንደ መሳፍንታዊ ስርዓት ራስን መስዋዕት የማድረግ ጠንካራ ዝንባሌ፤ በዲሞክራሲ ሊኖር አይችልም፡፡
በመሳፍንታዊ ስርዓት ጌታ እና ሎሌ በአንድ ቦታ አብረው አይኖሩም፡፡ ብዙውን ጊዜ፤ በሁለቱ መካከል የሚደረገው ንግግር በሦስተኛ ሰው አማካኝነት የሚከናወን ነው፡፡ ይሁንና አንዱ ሲጠቃ ሌላው ዘወትር ጠበቃ ሆኖ ይቆማል፡፡ በዲሞክራሲያዊ ስርዓት፤ ጌታ እና ሎሌ ተቀራርበው ይኖራሉ፡፡ በየዕለቱ ይገናኛሉ፡፡ ሆኖም አዕምሯቸው ውህደት የለውም፡፡ አንዱ ለአንደኛው ጥቅም መከበር ፀንቶ አይቆምም፡፡ ምክንያቱም፤ የዲሞክራሲ ስርዓት ጌታ እና ሎሌዎች የጋራ ሥራ ወይም ተልዕኮ እንጂ፤ መቼም ቢሆን የጋራ ጥቅም ሊኖራቸው አይችልም። በእንዲህ ዓይነት ህብረተሰብ፤ ሎሌው ሁልጊዜም ራሱን የሚመለከተው፤ በጌታው የመኖሪያ አካባቢ (መንደር) ለተወሰነ ሰዓት እንደመጣ ጎብኚ ነው፡፡ የጌቶቻቸውን አያት ወይም ቅድም አያት ቀይ ይሁኑ ጥቁር አያውቅም፡፡ አብሮ ኖሮ ቀጣይ ተወላጆቹን ሊያይ አይችልም፡፡ ለዘለቄታው ከእነሱ አገኛለሁ ብሎ የሚያስበው ነገርም የለውም፡፡ ታዲያ የእርሱን ህይወት ከእነርሱ ጋር አያይዞ ለማየት ምን ምክንያት ይኖረዋል? ጌታ የነበረው ሎሌ፤ ሎሌ የነበረው ደግሞ ጌታ ሊሆን የሚችልበት ዕድል አለ፡፡ የግንኙነታቸው መልክም ይቀያየራል፡፡
ቶኮቪሌ እንደጠቀሰው፤ በአሜሪካ ሰሜናዊ እና ደቡባዊ ክፍል በሚገኙ ግዛቶች ያለው ሁኔታ የተለያየ ነው፡፡ በሰሜኑ ባርነት ተወግዷል፡፡ በደቡቡ ገና እንደ ፀና ነው፡፡ ስለዚህ ስለ አሜሪካ ሲናገር ይህን ልዩነት ከግምት ሳያስገባ አይደለም። በሰሜኑ ከባርነት ነፃ የወጡ ሰዎች ወይም የእነሱ ልጆች ይገኛሉ። እነዚህ ሰዎች በማህበራዊ ምህዳሩ የሚሰጣቸው ግምት ወላዋይ ወይም እርግጠኝነት የሚጎድለው ነው። በህግ ደረጃ ከጌቶቻቸው እኩል ቦታ ይዘዋል። ሆኖም፤ በሐገሪቱ አያያዝ ፍፁም ዝቅ ያለ ቦታ እንዲይዙ ተደርገው ይገኛሉ፡፡ ራሳቸው ማህበራዊ ቦታቸውን በትክክል አያውቁትም፡፡ ይሁንና፤ ነፃነት እና እኩልነት የሰጣቸውን ፀጋ ይዘው፤ የኑሮ ሁኔታቸው የሰጣቸውን ግዴታ ተቀብለው፤ ሰዐት አክባሪነት እና ብቃት በሚታይበት አኳኋን ሥራቸውን በትክክል ያከናውናሉ፡፡
እነዚህ ሰዎች ያለ አንዳች ማቅማማት የሚታዘዙትን ይሰራሉ፡፡ ሆኖም፤ከቀጣሪያቸው ወይም ከሚያዛቸው ሰው በተፈጥሮ እንደሚያንሱ የሚያስቡ አይደሉም። እነዚህ ሰዎች የዲሞክራሲ ስርዐት የወለዳቸውን ባህርያት ተላብሰው፤ በነፃ ፈቃዳቸው የገቡበትን የሥራ ውል አክብረው፤ ሳይሸፍጡ በጀግንነት የሚኖሩ ናቸው። አዛዦቻቸውን ለማታለል ሳይሞክሩ፤ የሰጧቸውን የሥራ ኃላፊነት በአግባቡ የመወጣት የባህርይ ብቃት ያላቸው ራሳቸውን የሚያከብሩ ጀግኖች ናቸው። አዛዦቹም ከሠራተኞቻቸው የሚፈልጉት፤ የሥራ ውላቸውን አክብረው፤ በታማኝነት እና በትጋት እንዲሰሩላቸው እንጂ፤  እንዲያሸረግዱላቸው ወይም እንዲወዷቸው ወይም ‹‹እኔ ከርሱ ሌላ…›› የሚል ፍቅር እና  መስዋዕትነትን አይደለም፡፡ እንደ ሠራተኛ፤ ጥንቅቅ ያለ ሥራ እንዲሰሩ እና በሐቀኝነት እንዲያገልሏቸው ብቻ ይፈልጋሉ፡፡
ሆኖም ሠራተኞች፤ ቀጣሪያቸው በህይወታቸው ላይ ያን ያህል ስልጣን እንደ ሌለው ያውቃሉ፡፡ ይህን ሐቅ ጌታውም ያውቃል፡፡ ይህን መቀበል የሚቸግረው ሰው ግራ ይጋባል፡፡ ዘላቂ ሊሆን በማይችለው የሥራ ግንኙነት ውስጥ ሠራተኞቹ የማይለወጥ እና ዘላቂ ባህርይ እንዲያሳዩት ይመኛል፡፡ እንደ ቤት ሠራተኛ ቢሆኑለትም ይፈልጋል፡፡ ዕድሜ ልክ፤ ‹‹ራሳቸውን የማይችሉ›› የእርሱ አገልጋዮች መሆናቸውን ተቀብለው፤ በዚህም ኮርተው እንዲኖሩ ይሻል፡፡ ሆኖም አንድ ቀን ተቀጣሪ አገልጋይነታቸውን ትተው ቀጣሪ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
በመሣፍንታዊ ስርዐት ውስጥ እንዲህ ያለ ነገር የለም፡፡ ሁለቱም ወገኖች የያዙት ማህበራዊ ሥፍራ የማይለወጥ የእግዜር ስጦታ ነው፡፡ በመሳፍንታዊ ስርዐት ያለው አገልጋይነት ሰብእናን የሚያዋርድ ነው። በዲሞክራሲ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ነገር የለም። በዲሞክራሲ ስርዐት መቀጠር እንደመሳፍንታዊ ስርዓት አዋራጅ ባህርይ የለውም፡፡ ምክንያቱም፤ ግንኙነቱ በነፃ ፈቃድ የሚወሰን እና አገልጋይነቱም ጊዜአዊ ነው፡፡
በህዝብ ህሊና ውስጥ ተቀባይነት ያለው አስተሳሰብ፤ በቀጣሪ እና በተቀጣሪ መካከል ያለው መበላለጥ ጊዜያዊ እና ሊለወጥ የሚችል መሆኑን የሚቀበል አስተሳሰብ ነው፡፡
ሠራተኛው ታዛዥነትን የሚጠይቅ ግንኙነት ውስጥ እንደ ገባ ያውቃል፡፡ ግን ይህ ግንኙነት ጠቃሚ ሆኖ ስለታየው በነፃ ፈቃዱ የገባበት እና በርትቶ በመስራት ሊቀየር የሚችል ግኙነት መሆኑን ያምናል፡፡ አንዳንዴ፤ እኩልነቱ ከንቱ ህልም ሆኖ እየታየው ግራ ሊጋባ ይችላል፡፡
ስለዚህ አንዳንዴ በልቡ ያምፃል፡፡ ‹‹በእርግጥ እኩልነት የሚገኘው በዲሞክራሲ ክበብ ውስጥ ነው ወይስ ከዚያ ውጪ?›› የሚል ሐሳብ ሊፈጠርብት ይችላል። ጥቅም ስለሚያገኝበት ማገልገልን ይፈልጋል፤ ግን መታዘዝ ስላለ ቅር ሊሰኝ ይችላል፡፡ በዲሞክራሲ ስርዓት ውስጥ ያሉ ተቀጣሪዎች፤ ከአገልግሎት የሚገኘውን ጥቅም እንጂ አዛዣቸውን አይወዱትም። ‹‹በዲሞ ጨዋታ አይቆጡም ጌታ›› ማለት ይቻላል፡፡
መደምደሚያ
ብዙ ጭቆናዎች የተሳኩት፤ የጭቆና አገዛዞቹ በህዝቡ ዘንድ ህጋዊነት ወይም ተቀባይነት በማግኘታቸው ነው፡፡ ለምሳሌ፤ ባርነትን መውሰድ ይቻላል፡፡ እንደ ባርነት ያለ የከፋ አገዛዝ የለም፡፡ ጌታው በዚህ ስርዐት፤ ሰው እንደ ዕቃ ሊሸጥ ሊለወጥ ይችላል።
አስገራሚው ነገር፤ በሆነ መንገድ ለማመፅ እንኳን፤ በማሰብ ደረጃ እንኳን ተገዥዎች ለማመፅ የሚቸገሩበት ስርዐት ቢኖር የባርያ አሳዳሪ ስርዐት ነው፡፡ የባሪያ አሳዳሪ ስርዐት ታሪክን ብንመለከት፤ በሆነ መንገድ ስርዐቱ ፍፁም ተቀባይነት አግኝቶ ነበር፡፡ የሴቶችን የመብት ጥሰት ጉዳይ ተመልከቱ፤ አሁንም ተቀባይነት ያገኙ ጭቆናዎችን ትመለከታላችሁ፡፡  ጭቆና በህብረተሰቡ ዘንድ በሰፊው ተቀባይነት አግኝቶ፤ በሰዎች ህሊና ቅቡል ሆኖ፤ እንደ ተገቢ ጉዳይ ታይቶ ሊተገበር ይችላል፡፡ የሠራተኞችን ጉዳይ ተመልከቱ፡፡
በአሜሪካ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ምንዳ ለመቀበል መስራት ከባርነት (chattel slavery) ተለይቶ የሚታይ ጉዳይ አልነበረም፡፡ በአሜሪካ የእርስ በእርስ ጦርነት ዘመን ‹‹የሪፓብሊካን ፓርቲ›› የትግል መፈክር ‹‹ባርነትን›› (chattel slavery) ማጥፋት ነበር፡፡
ዘማቾቹ፤ ‹‹እኛ ተንቀሳቃሽ ባርነትን እና የምንዳ ባርነት እቃወማለን›› (We’re against chattel slavery and wage slavery) የሚል ነበር። በዘመኑ አስተሳሰብ፤ ነፃ ሰዎች ራሳቸውን ለሌሎች ሰዎች በኪራይ መልክ አይሸጡም፡፡
ምናልባት፤ አንድ ሰው ለጊዜው የሌሎች ተቀጣሪ ሊሆን ይችላል፡፡ አንድ ሰው የሌሎች ተቀጣሪ እና ታዛዥ የሚሆነው፤ በወቅቱ የአነጋር ፈሊጥ ‹‹ነፃ ሰው ወይም የራሱ ለመሆን በሚያደርገው የትግል ሂደት ነው፡፡››
በወቅቱ አስተሳሰብ፤ አንድ ነፃ ሰው የሚሆነው የሌሎችን ትዕዛዝ ለመፈፀም የማይገደድ ሰው ሲሆን ነው፡፡ ሰዎች ‹‹ራስን ማከራየት›› (to rent yourself) ተገቢ እና ነውር የሌለው ነገር ነው›› የሚለው እምነት ተቀባይነት እንዲያገኝ የማድረጉ ሥራ ብዙ ድካምን ጠይቋል፡፡ ከ150 ዓመታት በፊት ጨርሶ ተቀባይነት ያልነበረው ‹‹ራስን የማከራየት›› ጉዳይ ዛሬ ፍፁም ተቀባይነት አግኝቷል፡፡
አሁንማ ቀጣሪው ባለሐብት፤ የቀጠራቸው ሰዎች በትክክል እየሰሩ መሆናቸውን ለመቆጣጠር ብዙ ፍላጎት የለውም፡፡ ምክንያቱም፤ ራሱ ተቀጣሪው ራሱን የሚመራበት ሙያዊ የሥነ ምግባር ደንብ አውጥቶ ራሱን ለገዛ ደንቦቹ ተገዢ ስለሚያደርግ ክትትሉ ያን ያህል አስፈላጊ አይደለም። ስራውን ቢያጓድል፤ ከባለቤቱ በላይ የህሊና ወቀሳ የሚደርስበት እርሱ ይሆናል፡፡ ለውጡ ይህን ያህል ነው፡፡

Published in ጥበብ

በ2017 እኤአ ላይ የምዕራብ አፍሪካዋ ጋቦን ለምታስተናግደው 31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የሚደረጉት የምድብ ማጣርያ የመጀመርያ ዙር ጨዋታዎች ትናንት በመላው አፍሪካ ተጀምረዋል፡፡ ኢትዮጵያ በምድብ 10 ከሌሶቶ፤ ሲሸልስና አልጄርያ ጋር መደልደሏ ሲታወቅ፤ አራቱም ቡድኖች የምድብ ማጣርያውን የመጀመርያ ጨዋታዎቻቸውን በነገው እለት ያደርጋሉ፡፡ ኢትዮጵያ በባህርዳር ስታድዬም ሌሶቶን ስትገጥም፤  በአልጀርስ ከተማ በሚገኘው “ስታድ ሙስተፋ” ስታድዬም ደግሞ  አልጄርያ ሲሸልስን ታስተናግዳለች፡፡ የኢትዮጵያ እና የሌሶቶን ጨዋታ በመሃል ዳኝነት የሚመሩት ሴኔጋላዊው ማልኒንግ ዴይዲሁ እንደሆኑ ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያና ሌሶቶ ብሄራዊ ቡድኖች ሲገናኙ ከ20 ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል የባህርዳር ስታድዬም ለመጀመርያ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ የማጣርያ ጨዋታን የሚያስተናግድ ሲሆን የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን አህጉራዊ ግጥሚያዎችን የማካሄድ ፈቃድ የሰጠው ዘንድሮ ነው፡፡ ስታድዬሙ ከወራት በፊት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደደቢት በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ እና በኮንፌደሬሽን ካፕ ያደረጓቸውን ጨዋታዎችን በከፍተኛ ድምቀት እንዳስተናገደ ይታወቃል። መደበኛው የብሄራዊ ቡድን መጫወቻ የነበረው የአዲስ አበባ ስታድዬም በተደራራቢ ግጥሚያዎች እና በወቅቱ የአየር ሁኔታ አመቺ ሆኖ ባለመገኘቱ ባህርዳር ስታድዬም ተመራጭ ሆኗል፡፡  የኢትዮጵያና የሌሶቶ ብሄራዊ ቡድኖችን ጨዋታን በባህርዳር ስታድዬም ተገኝቶ ለመከታተል በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ የተገለፀው ዝቅተኛ 50 ብር ከፍተኛ 700 ብር የትኬት ዋጋ ሰሞኑን ሲያነጋግር ነበር፡፡ የዋጋው መወደድ በከተማው ነዋሪዎች ላይ ቅሬታ ከመፍጠሩም በላይ አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች ስታድዬሙ ለመጀመርያ ጊዜ የብሄራዊ ቡድን ጨዋታ እንደማስተናገዱ ለዋልያዎቹ አስፈላጊ ድጋፍ እንዲገኝ የስታድዬም መግቢያው ለከተማው ነዋሪ በነፃ እንዲሆን ጠይቀው ነበር፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ከየአቅጣጫው የቀረቡትን አስተያየቶች በማገናዘብ አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት ዝቅተኛውን የስታድዬም መግቢያ ዋጋም 10ብር አድርጎታል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለጨዋታው ከባለፈው ሰኞ ጀምሮ ባህርዳር በመግባት ልምምዱን እየሰራ ቆይቷል፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ ወደ ባህርዳር ከመጓዙ በፊት እዚህ አዲስ አበባ ላይ የመጀመርያውን የአቋም መፈተሻ ግጥሚያ ከዛምቢያ አቻው በማድረግ 1ለ0 ተሸንፎ ነበር። በወዳጅነት ጨዋታው አዲሱ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ በርካታ አዳዲስ ዋልያዎችን አሰልፈዋል፡፡ ዋልያዎቹ ከዛምቢያ አቻ ሊሆኑበት የሚያስችል እድልም ነበር፡፡ በ83ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ቅጣት የቡድኑ ብቸኛ አጥቂ ቢኒያም አሰፋ ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡ በነገው ጨዋታ ምናልባትም ብሄራዊ ቡድኑ በአጥቂ መስመር ክፍተት ሊኖርበት ይችላል የሚል ስጋት ነበር  ከዛምቢያ ጋር ከተካሄደው የወዳጅነት ጨዋታ በኋላ ተስፋ የሚያሳድሩ ነገሮች ተከስተዋል፡፡ በግብፁ ክለብ አልሃሊ የሚጫወተው ሳላዲን ሰኢድ ባለፈው ማክሰኞ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ በዚያው ቀን ቡድኑን በባህርዳር ተቀላቅሏል፡፡ በሌላ በኩል በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው ጌታነህ ከበደ እና ከግብፅ የመጡት ኡመድ ኡክሪና ሽመልስ በቀለ ከዛምቢያ ጋር የተደረገውን የወዳጅነት ጨዋታ በአዲስ አበባ ተገኝተው ከተከታተሉ በኋላ ቡድኑን በመቀላቀል ካለፈው ሰኞ ጀምሮ በባህርዳር ስታድዬም ልምምድ በመስራት ላይ ናቸው፡፡
የሌሶቶ ብሄራዊ ቡድን ከወር በፊት በ2015 የደቡብ አፍሪካ አገራት ሻምፒዮና ተሳታፊ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ከነገው ጨዋታ በፊት በኮሳፋ ፓፕ ሶስት ግጥሚያዎች እንዲሁም ከሳምንት በፊት በወዳጅነት ጨዋታ 1 ተጨማሪ ግጥሚያ በማድረግ ከኢትዮጵያ ጋር ለሚያደርገው ግጥሚያ የተሟሟቀ ዝግጅት ነበረው፡፡ በኮሳፋ ካፕ በምድብ 2 ከማዳጋስካር፤ ከስዊዚላንድ እና ከታንዛኒያ ጋር ተደልድሎ የነበረው የሌሶቶ ቡድን በመጀመርያዎቹ ሁለት የምድብ ጨዋታዎች በማጋዳጋስካር 2ለ1 እንዲሁም በስዋዚላንድ 2ለ0 ቢሸነፍም በምድቡ የመጨረሻ ጨዋታ ታንዛኒያን 1ለ0 ማሸነፍ ችሏል፡፡ ከሳምንት በፊት ደግሞ ከላይቤርያ ጋር ባደረገው የወዳጅነት ጨዋታ 2ለ0 በማሸነፍ በጥሩ ብቃት ላይ እንደሚገኝ አረጋግጧል፡፡ ዋና አሰልጣኙ  ሴፊ ማቴቴ ቡድናቸው ከኢትዮጵያ ጋር ለሚያደርገው ጨዋታ በአካል ብቃት እና በስነልቦና ጥሩ መዘጋጀቱን ሰሞኑን ተናግረዋል፡፡ ስታር አፍሪካ እንደዘገበው ሌሶቶ ከኢትዮጵያ ጋር ከ20 ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ እንደምትገናኝ ተገልፆ፤ አሰልጣኙ በምድብ ማጣርያው የመጀመርያ ጨዋታ ከኢትዮጵያ ከባድ ፈተና ሊገጥመን ቢችልም በአበረታች ውጤት አጀማመራችን ለማሳመር ፍላጎት አለን ብለዋል፡፡
የሌሶቶ ብሄራዊ ቡድን አዞዎቹ በሚል ቅፅል ስሙ የሚታወቅ ነው፡፡ ቡድኑን በዋና አምበልነት የሚመራው ለሌችስተንስታይኑ ክለብ ኤፍሲ ብሌዘርስ በአማካይ መስመር የሚጫወተው ራሌኮቲ ሞካሃላኔ ነው፡፡ በአመዛኙ በአገር ውስጥ ክለቦች በሚጫወቱ ወጣት ተጨዋቾች የተገነባው የሌሶቶ ቡድን በስብስቡ አምበሉን ጨምሮ በተለይ በአማካይ እና አጥቂ መስመሮች ከ10 በላይ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾችን ከተለያዩ ዓለም ክፍሎች በማሰባሰብ አካትቷል፡፡ ቀላቅሏል፡፡
ከእነዚህ ፕሮፌሽናሎቹ መካከል የመጀመርያው ተጠቃሽ አምበሉ ራሌኮቲ ሲሆን ሌሎቹ፤ ለደቡብ አፍሪካው ክለብ ብሎምፎንቴን ኤፍሲ የሚጫወተው ተከላካዩ ሴፒሪቲ ማሌፋኔ፤ ለአልጄርያው ክለብ ኤምሲ ሳይዳ የሚጫወተው አማካዩ ሞትላሌፑላ ሞፎሎ፤ለደቡብ አፍሪካው ሃይላንድ ፓርክ የሚጫወተው አማካዩ ቱሜሎ ቤራንግ ለደቡብ አፍሪካው ሳንቶስ የሚጫወተው አማካዩ ካቴልሆ ሞሌኮ፤ ለደቡብ አፍሪካው ማሉቲ ኤፍኢቲ ኮሌጅ የሚጫወትው አጥቂው ሴፖሌኮሃና፤ ለአንዶራው ኤፍሲ አንዶራ የሚጫወተው አጥቂው ሳፌሎ ቴሌ፤ ለአሜሪካው ዊልኒንግተን ሃመር ሄድስ በአጥቂ መስመር የሚሰለፈው ሰኒ ጃኒ እንዲሁም ለቦትስዋናው ዲፌንስ ፎርስ አጥቂ ሆኖ የሚጫወተው ሌሃሎሜላ ራምቤሌ ናቸው፡፡

 ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ ኩባንያ ጋር በመተባበር ነገ የሚያካሂዱት የ7.5 ኪ.ሜ ሩጫ ውድድር በአሯሯጮች እንደሚታጀብ ተገለፀ፡፡
በውድድሩ አሯሯጮችን መመደብ ያስፈለገው የጤና ሯጮች በውድድሩ ላይ ወጥ በሆነና አቅማቸውን ባገናዘበ መልኩ እንዲሮጡ ለመርዳት ነው ተብሏል። በአትሌቲክሱም ዓለም አሯሯጮች በብዛት ሪከርድ እንዲሰበር እንደሚያግዙ የሚጠቅሰው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ መግለጫ በውድድሩ ጤና ሯጮች በአቅማቸውና ውድድሩን ሳይሰለቹ እንዲጨርሱ እንደሚያግዝ አመልክቷል፡፡ ከጤና ሯጮች ባሻገር የጎዳና ላይ ሩጫው በአጠቃላይ ከ700 በላይ የክለብ እና የግል ተወዳዳሪ አትሌቶች ይፎካከሩበታል፡፡
ዳሳኒ የጎዳና ላይ ሩጫ ከ10ሺ በላይ ተሳታፊዎች እንደሚሳተፉበት የሚጠበቅ ሲሆን፤ ለአሸናፊ አትሌት የሚበረከተውን 60ሺ ብር ሽልማት ጨምሮ በአጠቃላይ ወደ 300ሺ ብር የሽልማት ገንዘብ በየደረጃው ለሚመዘገቡ ውጤቶች እንደሚሰጥ ታውቋል፡፡

ብራንዱ ላይ ከ500 ሚ. -1 ቢ.ዶላር ኪሳራ ደርሷል፡፡ ብላተር ይታሠሩ ይሆናል፡፡
ኢሳ ሃያቱ በጊዜያዊ ፕሬዝዳንትነት ሊሾሙ ይችላሉ፡፡
      ዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበር የተናወጠበት የሙስና ቀውስ  ሰሞኑን የበረደ ቢመስልም እንደገና በአነጋጋሪ ሁኔታዎች ማገርሸቱ አይቀርም፡፡
ከሳምንት በፊት ፎርብስ መፅሄት በሰራው ስሌት የሙስና ቀውሱ የፊፋ የብራንድ ዋጋን በ500 ሚሊዮን ዶላር እንዳሽቆለቆለው ያመለከተ ሲሆን፤ አንዳንድ ትንታኔዎች በበኩላቸው የብራንድ ኪሳራው እስከ 1 ቢሊዮን ዶላር ሊደርስ እንደሚችል ገልፀዋል፡፡ ሰሞኑን የስዊዘርላንድ አቃቤ ህግ ዙሪክ ውስጥ የሚገኘውን የፊፋ ዋና መ/ቤት በድንገት በመጐብኘት በፕሬዝዳንቱ ሴፕ ብላተር እና በዋና ፀሐፊያቸው ዥሮሜ ቫልክ ቢሮ የሚገኙትን ኮምፒዩተሮችና መረጃዎቻቸውን ሰብስቦ ወስዷል። የስዊዘርላንድ መንግስት በ2018 ራሽያ በ2022 ኳታር እንዲያዘጋጇቸው የተፈቀዱላቸው ሁለት ዓለም ዋንጫዎች በሙስና ተሰጥተዋል በሚለው ምርመራ ከፍተኛ ክትትል ማድረጉን ቀጥሏል። የመስተንግዶ ምርጫው በሙስና መካሄዱ ከተረጋገጠ ሁለቱም አገራት አዘጋጅነታቸውን ይነጠቃሉ ተብሎም እየተዘገበ ነው፡፡ ስዊዘርላንዳዊው ሴፕ ብላተር ከሁለት ሳምንት በፊት ለአምስተኛ የስራ ዘመን ፊፋን በፕሬዝዳንትነት ለመምራት ቢመረጡም ከ4 ቀናት በኋላ ስልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው  መልቀቃቸው አይዘነጋም፡፡ በመላው ዓለም በሚገኙ የስፖርት አመራሮች፤ በእውቅ እግር ኳሰኞች ፤ በሚዲያው ፤ በስፖንሰሮች እና በስፖርት አፍቃሪው የሴፕ ብላተር ስልጣን ለመልቀቅ ፈቃደኛ መሆን የተቋሙ ስርነቀል መለወጥን   ያሳየ ርምጃ ሲባል ሰንብቷል፡፡ ከሳምንቱ አጋማሽ ጀምሮ ግን በተለያዩ የአውሮፓ አገራት ውስጥ የሚሰሩ የህግ ባለሙያዎችና ተቋማት ግን ፕሬዝዳንቱ  ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ ስራ እንዲያቆሙ እየጠየቁ ናቸው፡፡ ብላተር ስልጣናቸውን ለመልቀቅ ፈቃደኛ የሆኑት ከእስር ለማምለጥ ነው ብለውም ይተቻሉ፡፡
ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ሴፕ ብላተርን የሚተካ የፕሬዝዳንት ምርጫ ለማከናወን እስከ 10 ወራት ሊቆይ እንደሚችል በአንዳንድ ዘገባዎች ጐን ለጐን እየተገለፀ ነው፡፡ ሴፕ ብላተር ስልጣናቸውን ከዚያ በፊት እንዲለቅቁ ከተደረገ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ኢሳ ሃያቱ በሽግግር ጊዜ ፕሬዝዳንትነት ጊያዊ ሹመት ሊሰጣቸው ይችላል፡፡ ሴፕ ብላተርን ለመተካት እጩ ሆነው ከቀረቡት የእግር ኳስ ከፍተኛ አመራሮች በፕሬዝዳንት ምርጫው በብቸኝነት የተፎካከሯቸው የዮርዳኖስ ልዑል አልቢን ዋናው ናቸው፡፡ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ፕሬዝዳንት ሚሸል ፕላቲኒም ታጭቷል፡፡ ብላተርን ለመፎካከር ሞክረው ራሳቸውን ከምርጫ ያገለሉት የሆላንድ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ማይክል ቫን ፕራግም ተጠቁመዋል፡፡ የቀድሞዎቹ የእግር ኳስ ኮከቦች እነ ማራዶና፤ ዚኮ ዊሃና ሌሎችም ተጠቁመዋል፡፡ ማራዶና ፕሬዝዳንት ቢሆን ድጋፍ እንደምትሰጥ ቬንዝዋላ የገለፀች ሲሆን ጆርጅ ዊሃ በበኩሉ ለመጀመርያ ጊዜ አፍሪካዊ የፊፋ ፕሬዝዳንት መመረጥ ይኖርበታል በሚል ሃሳብ ድምፁን አሰምቷል
የብላተር እጣ ፋንታ
ሴፕ ብላተር ለአምስተኛ የስራ ዘመን ፊፋን እንዲመሩ በተመረጡበት ወቅት በመጀመርያ ዙር ድምፅ አሰጣጥ 133 ድምፅ አግኝተዋል፡፡ ተቀናቃኛቸው የነበሩት የዮርዳኖስ ልዑል አልቢን 73 አግኝተው ወደ ሁለተኛ ዙር ላለመግባት ወስነው ከፉክክሩ በመውጣታቸው ሊያሸንፉ መቻላቸው አይዘነጋም ነበር፡፡ በፕሬዝዳንትነት ምርጫው ሴፕ ብላተር የአፍሪካና የኤስያ እግር ኳስ ፌደሬሽኖችን የበዛ ድጋፍ ቢያገኙም ከአሜሪካ፤ ከደቡብ አሜሪካ እና ከአውሮፓ ዞኖች ወሳኙን ድጋፍ አጥተዋል፡፡ በፕሬዝዳንትነት ቢቀጥሉም ብዙም መስራት እንደማይችሉ ሴፕ ብላተር በመረዳታቸው በተመረጡ በአራተኛ ቀናቸው ስልጣኔን እለቃለሁ ብለው መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር የሙስና ቀውስ መላውን ዓለም ላለፉት ሶስት ሳምንታት ሲያነጋግር ከተነሱ ጥያቄዎች ቀጣዩ የፊፋ ሁኔታ እንዴት ይሆናል የሚለው ነው፡፡ ብዙዎች አስተያየት ሰጭዎች ፊፋ በአሰራሩ ግልፅ እና ተጠያቂነት የሞላበት አሰራር እንዲከተል፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነበረውን ተዓማኒነት በማይናወፅ መሰረት ላይ የሚገነቡ አዳዲስ አመራሮች እንዲፈጠሩበት እየመከሩ ናቸው፡፡ የፊፋን አጠቃላይ የስራ ሂደት የሚከታተል እና የሚቆጣጠር ፉትቦል ትሩዝ ኮሚሽን እንዲፈጠርም ሃሳብ ያቀረቡም አሉ፡፡
ሴፕ ብላተር የፊፋ ፕሬዝዳንት ሆነው ለ17 አመታት ሰርተዋል፡፡ በሰሩባቸው 17 የስልጣን ዓመታት ፊፋ 12 ቢሊዮን ዶላር ካፒታል ማንቀሳቀስ መቻሉ፤ ከዓለም ህዝብ 1.6 ቢሊዮን ያህሉ ከስፖርቱ ጋር በተለያየ መንገድ መተሳሰሩ፤ አንድ ዓለም ዋንጫ እስከ 2 ቢሊዮን ዶላር እንዲያተርፍ መቻሉ፤ በአፍሪካ ፤ በኤሽያ እና በሌሎች የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ትናንሽ እና ደሃ አገራት ከስፖርቱ እኩል ተጠቃሚ መሆናቸው እንደታላቅ ስኬቶቻቸው ተወስቶላቸዋል፡፡
ፊፋን ያስጨነቁት ጫናዎች
ብላተር እና የቅርብ ረዳታቸው ዋና ፀሃፊ ዠሮሜ ቫልከ አነካክቷል የተባለው የሙስና መረብ በ2010 እኤአ ላይ አፍሪካ 19ኛውን ዓለም ዋንጫ በደቡብ አፍሪካ ለመጀመርያ ግዜ ያስተናገደችበት ሁኔታ ነው፡፡ ደቡብ አፍሪካ ይህን ዕድል ለማግኘት 10 ሚሊዮን ዶላር በሰሜን፤ አሜሪካ እና የካርቢያን አገራት እግር ኳስ ፌደሬሽኖች በጉቦ መልክ እንደተከፋፈለ በኤፍቢአይ እየቀረበ ያለው ክስ የመጀመሪያው ጫና ነው፡፡
ሌሎች ጫናዎች የመጡት የፊፋ የቀድሞ አመራሮች በሚሰጧቸው የኑዛዜ መግለጫዎች ነው፡፡ የፊፋ የቀድሞ ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት ጃክ ዋርነር ፊፋ 19ኛው ዓለም ዋንጫ በደቡብ አፍሪካ እንዲዘጋጅ ለደቡብ አሜሪካ አገራት ፌደሬሽኖች ለጉቦ የተሰጠውን ገንዘብ ብላተር እንዳዘዙ እመሰክራለሁ ብለዋል፡፡ የቀድሞ የሰሜን እና መካከለኛው አሜሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ኮንካፍ ፕሬዝዳንት የነበሩትና በስፖንሰርሺፕ እና የማርኬቲንግ ድርድሮች ከፍተኛ ሚና የነበራቸው ቻርልስ ብሌዘር ደግሞ የፊፋን የሙስና መረብ የሚያጋልጥ ምስክርነት ከ2 ዓመት በፊት ለኤፍቢአይ መስጠታቸው ባለፈው ሰሞን መገለፁ ዓለም አቀፉን የእግር ኳስ ማህበር ከላይ እስከታች አናግቶታል፡፡ እንደ አሜሪካው የደህንነት ተቋም ኤፍ ቢአይ ጥልቅ ምርመራ በዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበር አማካኝነት 4 ዓለም ዋንጫዎች አዘጋጅ የተመረጠላቸው በውስብስብ የሙስና መረብ መሆኑን ተደርሶበታል፡፡ እነዚህ 4 ዓለም ዋንጫዎች በ1998 ፈረንሳይ፤ በ2010 ደቡብ አፍሪካ ያዘጋጇቸውና፤ በ2018 ራሽያ እና በ2022 እኤአ ኳታር የሚያዘጋጇቸው ናቸው፡፡
ቻርልስ ብሌዘር የተባሉ የቀድሞ የፊፋ አመራር ከ2 አመት በፊት ብሩክሊን ውስጥ በዝግ ችሎት በሰጡት የእምነት ቃል ለ1998 እና ለ2010 ሁለት ዓለም ዋንጫዎች በፊፋ ውስጥ ያሉ ከፍተኛ ባለስልጣና የአባል አገራት ፌደሬሽኖች አመራሮች ጉቦ መቀበላቸውን በመናገር ጥፋተኝነታቸውን መግለፃቸው ይፋ የሆነው የብላተር ስልጣን መልቀቅ በተሰማ በማግስቱ ነበር፡፡ በፊፋ ዓለም አቀፍ የስፖንሰርሺፕ ድርድሮች ከፍተኛ ሚና የነበራቸው ቻርልስ ብሌዘር በ10 ክሶች ጥፋተኛ ነኝ ብለው የእምነት ቃላቸውን በመስጠታቸው እስከ 20 ዓመት ጽኑ እስራት ይጠብቃቸዋል፡፡
እንግሊዝ፤ አሜሪካ እና በርካታ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር አገራት ሴፕ ብላተር ከተመረጡ ከዓለም ዋንጫ ውድድር ራሳችንን እናገላለን ብለው አቋም መውሰዳቸው በፊፋ ላይ ትልቁን ጫና እንደፈጠረም ይነገራል፡፡ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር የሻምፒዮንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ በተካሄደበት እለት ተሰብስቦ ተሰብስቦ የብላተር መመረጥን ለማውገዝ እና ከዓለም ዋንጫ ውድድር ለመውጣት ውሳኔዎችን ለማሳለፍ እቅድ ሁሉ ነበረው፡፡ ከስብሰባ ሁለት ቀናት ቀደም ብሎ ግን ብላተር በገዛ ፈቃዳቸው ስልጣናቸውን እንደሚለቁ በመግለፃቸው የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ጠርቶት የነበረውን አስቸኳይ ስብሰባ ትቶታል፡፡ ሴፕ ብላተር ለአምስተኛ የስራ ዘመን በተመረጡ ማግስት ፊፋ የአውሮፓ አገራት በ2026 የሚደረገውን 23ኛው የዓለም ዋንጫ ለማዘጋጀት ሊወዳደሩ እንደሚችሉ ቢያሳውቅም ይህ እቅድ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም ሰሞኑን ተወስኗል፡፡
ባለፉት አራት ዓመታት ፊፋ በተለይ ከዓለም ዋንጫ ጋር በተያያዘ እስከ 5.72 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ነበረው፡፡ አብዛኛው የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበር ገቢ በአውሮፓ እና በአሜሪካ አህጉራት የሚገባ ስለሆነ ከዓለም ዋንጫ ራሳቸውን ቢያገሉ ኖሮ ፊፋ ከባድ ክስረት ይገጥመው ነበር፡፡ በአንድ ዓለም ዋንጫ ከሚሳተፉ 32 አገራት 13 ከአውሮፓ አህጉር የሚወከሉ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የአውሮፓ ክለቦች ፊፋ ከዝውውር ገበያው የሚያገኘውን ገቢ 57 በመቶ ድርሻ በመውሰድም ትልቅ አስተዋፅኦ አላቸው፡፡ እስከ ብራዚሉ 20 ኛው አለም ዋንጫ 11 ያሸነፉት የአውሮፓ አገራት ናቸው፡፡ በአንድ ዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ ከሚገቡ 32 አገራት ብሄራዊ ቡድኖች 563 ተጨዋቾች ወይም 76 በመቶው በአውሮፓ አገራት ክለቦች የሚጫወቱ ናቸው፡፡ ከዓለም ዋንጫ ተመልካቾች 36 በመቶው ከአውሮፓ ይገኛሉ፡፡

  - አንድ ደብዳቤው ከ3 አመታት በፊት 3ሚ ዶላር ተሽጧል
   ታዋቂው የፊዚክስ ሊቅ አልበርት አንስታይን በተለያዩ ጊዜያት የጻፋቸው ደብዳቤዎች በቀጣዩ ሳምንት ሎሳንጀለስ ውስጥ ለጨረታ እንደሚቀርቡና ከ1 ሚሊዮን ዶላር በላይ ይሸጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ዘ ቴሌግራፍ ዘገበ፡፡
ለጨረታ የሚቀርቡት ደብዳቤዎች በአንስታይን የእጅ ጽሁፍ የተጻፉና በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ እንደሆኑ የጠቆመው ዘገባው፣ ከደብዳቤዎቹ መካከልም አንስታይን ለልጆቹና ሃንስ እና ኤድዋርድ እንዲሁም ለቀድሞ የትዳር አጋሩ ሜሊቫ ማሪክ የጻፋቸው ይገኙበታል ብሏል፡፡
አልበርት አንስታይን በደብዳቤዎቹ ፈጣሪን፣ ፖለቲካን፣ ታሪክን፣ ሳይንስንና ሌሎች ጉዳዮቹን የተመለከቱ ሃሳቦቹን እንዳንጸባረቀና የሳይንቲስቱን የአመለካከት ጥልቀት የሚያሳዩ አስገራሚ ሰነዶች እንደሆኑ፣ ጨረታውን ያዘጋጀው የሎሳንጀለስ አጫራች ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጆሴፍ ማዳሌና ተናግረዋል፡፡
አንስታይን ሃይማኖትን በተመለከተ የጻፈውና ጎድ ሌተር በመባል የሚታወቀው ደብዳቤ እ.ኤ.አ በ2012 ለጨረታ ቀርቦ በ3 ሚሊዮን ዶላር መሸጡንም ዘገባው አስታውሷል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

 የዚምባቡዌው ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ፤ የእንጀራ ልጅ ረስል ጎሬራዛ ባለፈው የካቲት በመዲናዋ ሃራሬ ማንነቱ ያልተገለጸን ግለሰብ በመኪናው ውስጥ ገድሏል በሚል ተከሶ ፍርድ ቤት መቅረቡንና ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ 800 ዶላር እንዲከፍል እንደተፈረደበት ቢቢሲ ዘገበ፡፡
የቀዳማዊት እመቤት ግሬስ ሙጋቤ የበኸር ልጅ የሆነው የ31 አመቱ ጎሬራዛ፣ በሃራሬ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርቦ ድርጊቱን መፈጸሙን በማመን እንደተጸጸተ ገልጾ፣ ይቅርታ እንዲደረግለት ጠይቋል። ፍርድ ቤቱም የመንጃ ፈቃዱን ነጥቆ እስር ቤት ሊወረውረው ቢያስብም፣ መጸጸቱን አይቶ በገንዘብ ቅጣት ብቻ እንዳለፈው አስታውቋል፡፡
ግለሰቡ በእስር አለመቀጣቱ በርካታ የመዲናዋ ነዋሪዎችን እንዳስደነገጠ የገለጸው ዘገባው፣ በተመሳሳይ ወንጀል የተከሰሱ ሌሎች ወንጀለኞች በሁለት አመታት እስር እንደተቀጡ አስታውሷል፡፡
ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ማስተላለፉን ተከትሎ የእስር ቤቱ ሃላፊዎች ተከሳሹን በደንቡ መሰረት ከፍርድ ቤቱ ወደ ነበረበት እስር ቤት በመውሰድ የተቀጣውን የገንዘብ ቅጣት ከከፈለ በኋላ እንዲለቀቅ ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ፣ የመንግስት የደህንነት አካላት ሊከላከሏቸው እንደሞከሩም ዘገባው አክሎ ገልጧል።

Published in ከአለም ዙሪያ

 - በእስር ቤቱ የ150 አመት ታሪክ ሲያመልጡ የመጀመሪያዎቹ ናቸው
  - ድንበር አቋርጠው ወደ ካናዳ ሳይገቡ አልቀሩም ተብሏል
     የኒውዮርክ አገረ ገዢ አንድሪው ኮሞ ባለፈው አርብ ሌሊት ዳኔሞራ በተባለችው ከተማ ከሚገኝ እስር ቤት ያመለጡትን ሁለት ነፍሰ ገዳዮች በተመለከተ መረጃ ለሰጣት ሰው፣ ግዛቲቱ 100 ሺህ ዶላር ወሮታ እንደምትከፍል ማስታወቃቸውን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ሪቻርድ ማት እና ዴቪድ ስዊት የተባሉት እነዚህ አደገኛ ነፍሰ ገዳዮች ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግለት በዚህ እስር ቤት የ150 አመታት ታሪክ አምልጠው መጥፋት የቻሉ የመጀመሪያዎቹ ታራሚዎች ናቸው ያለው ዘገባው፤የታሰሩበትን ክፍል የብረት ግድግዳ በመቁረጥ በፍሳሽ ማስተላለፊያ ቱቦዎች ውስጥ ለውስጥ ሾልከው እንዳመለጡ ገልጧል፡፡
“እነዚህ ነፍሰ በላዎች አሁንም የከፋ ወንጀል ከመፈጸም ወደኋላ የማይሉ ናቸው” ብለዋል፤አገረ ገዢው አንድሪው ኮሞ፣ ምናልባትም እስረኞቹ ድንበር አቋርጠው ወደ ካናዳ ሳይገቡ እንዳልቀሩ ግምታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ሁለቱ እስረኞች ማምለጣቸውን ተከትሎ፣ ፖሊስ በአካባቢው የሚገኙ ጎዳናዎችን ዝግ አድርጎ ጉዳዩን በጥብቅ መመርመሩንና  በግዛቲቱ የሚደረገው የደህንነት ፍተሻና ፍለጋ በከፍተኛ ሁኔታ ተጧጡፎ መቀጠሉን የገለጸው ዘገባው፣ ከ200 በላይ ፖሊሶችም በአነፍናፊ ውሾችና በአየር ላይ አሰሳ በታገዘ እስረኞቹን የማደን ስራ መጠመዳቸውን አስረድቷል፡፡
ሪቻርድ ማት አንድን ግለሰብ በማገትና በመግደል ወንጀል ተከሶ የ25 አመታት የእስር ቅጣት ላይ እንደነበርና፣ ዴቪድ ስዊትም አንድን የፖሊስ ሃላፊ በመግደሉ የእድሜ ልክ እስር ፍርደኛ እንደነበር ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ