Saturday, 20 June 2015 11:11

የፀሐፍት ጥግ

ስለትወና)
ትወና፤ የሌሎችን ሰብዕና የመውሰድና የራስህን ጥቂት ተመክሮ የማከል ጉዳይ ነው።
ዣን ፖል ሳርተር
ተዋናይ ለመሆን ህንፃ መሆን አለብህ፡፡
ፖል ኒውማን
ትወና ስሜታዊነት አይደለም፤ ስሜትን በተሟላ መንገድ መግለፅ መቻል እንጂ፡፡
ቶማስ ሬይድ
ሥነ ጥበብ እጃችን፣ ጭንቅላታችንና ልባችን እንደ አንድ ሆነው የሚጣመሩበት ነው፡፡
ጆን ሩስኪን
ትወና ደስ የሚል ስቃይ ነው፡፡
ዣን ፖል ሳርተር
ትወና ከሞላ ጎደል ከጨዋታ በላይ አይደለም። ሃሳቡም ህይወትን ሰዋዊ ማድረግ ነው፡፡
ጄፍ ጎድልብሊም
የትወና ጥበብ ሰዎች እንዳያስሉ ማድረግንም ይጨምራል፡፡
ራልፍ ሪቻርድሰን
ትወና እወዳለሁ፤ ምክንያቱም ህልም እውን የሚሆንበት፣ ቅዠት ህይወት የሚዘራበትና የሚቻለው ነገር ሁሉ ገደብ የሌለበት በመሆኑ ነው፡፡
ጄሲካ አልባ
ራሴን ለፍቅረኛ እንደምሰጠው ነው ለገፀባህርያቶቼ የምሰጠው፡፡
ቫኔሳ ሬድግሬቭ
ተዋናይ ህይወትን መተርጎም አለበት፤ ያንን ለማድረግ ደግሞ ህይወት የምትሰጠውን ተመክሮ ሁሉ በፀጋ ለመቀበል ፈቃደኛ መሆን ይኖርበታል፡፡
ማርሎን ብራንዶ
ተዋናዮች ከህይወት በላይ መግዘፍ አለባቸው። በዕለት ተዕለት ህይወት ከብዙ ተራና እዚህ ግቡ የማይባሉ ሰዎች ጋር ትገናኛላችሁ፡፡ በመድረክም ላይ ከእነሱ ጋር የምትጋፉበት ምክንያት አይታየኝም፡፡
ኒኖን ዲ ሌንክሎስ
የታላቅ ተዋናይ መሰረታዊ ጉዳይ በትወና ውስጥ ራሱን መውደዱ ነው፡፡
ቻርሊ ቻፕሊን

Published in የግጥም ጥግ

ባለፈው እሁድ የተጠናቀቀው የጌም ኦፍ ትሮንስ 5ኛ ሲዝን፣ ካለፉት አመታት የላቀና መታየት የሚገባው ምርጥ የቴሌቪዥን ድራማ ነው - በተለይ ለዘመናችን፣ በተለይ ለአገራችን ቁልፍ በሆኑ ዋና ዋና ጥያቄዎች ዙሪያ ያጠነጠነ ድራማ መሆኑ አስደንቆኛል። የድራማው ዋና ዋና የታሪክ ሰንሰለቶችንና ዋና ባለታሪኮቹን እየጠቃቀስኩ ለማስቃኘት ልሞክር።

1. ጉልበትንና እምነትን፣ ሃይማኖትንና ቤተመንግስትን ማደባለቅ።  
ሰርሲ ላኒስተር፣ ንግስት ናት። ልጇ በቅርቡ ዘውድ ቢጭንም ገና ላቅመአዳም ስላልደረሰ፣ እቴጌ ሰርሲ የንጉሡ ሞግዚት፣ አማካሪና እንደራሴ ሆናለች። በዚህ ትልቅ ስልጣን ዙሪያ፣ በርካታ የስጋት፣ የጥርጣሬና የጥላቻ ጦሮች የከበቧት ይመስላታል። አምርራ ከምትጠላቸውና እንደ ደመኛዋ ከምታያቸው ሰዎች መካከል፣ ወንድሟ ቲርዮን ላኒስተር ነው። ቲርዮን፣ ድንክ በመሆኑ የንግሥና ተስፋ እንደሌለው እርግጠኛ ናት። ግን፣ እንደፈለገች የሚሽከረከርላትና የሚታዘዝላት አይነት ሰው አይደለም። ብልህነቱና የንግግር ችሎታው ያስጠላታል። የንጉሡ ዋና አማካሪ መሆን እንደማያቅተው ስለምታውቅም፣ እንደ ተቀናቃኝ ነው የምታየው።
“ደግነቱ” እንከን የለሽ አይደለም። አለቅጥ የመጠጣትና የመስከር፣ እናም በዘፈቀደ ሕይወቱን የማባከን ዝንባሌ አለበት። እንደለመደው ሴቶችን እያንጋጋ “ሲንዘላዘል”፣ በአጋጣሚ ከአንዲት ሴት ጋር ከተዋወቀ በኋላ ግን በፍቅር ባነነ። በትሹም ቢሆን፣ ሕይወቱን ስርዓት የማስያዝ ጉልበት አገኘ - በፍቅር ሃይል።
ግን፣ የንጉሥ ቤተሰብ ነው። የቱንም ያህል በፍቅር ሕይወቱ ቢታደስ፣ ከተራ ሴት ጋር ተጋብቶ አብሮ እንዲኖር አይፈቀድለትም። የቤተሰብን ክብር ይነካል። ይሄ ለሰርሲ ጥሩ ሰበብ ነው - ወንድሟን ክፉኛ ለማቁሰል ይጠቅማታል። “ለቤተሰቡ ክብር ሲል ከሚያፈቅራት ሴት መለየትና መሥዋዕት መክፈል አለበት” በማለት የወንድሟን ሕይወት ለማናጋት አልከበዳትም። ደግሞም ተሳክቶላታል።
ምን ዋጋ አለው? በጥላቻ የተመረዘ ነፍስ፣ አንድ ሁለቴ በማጥቃት አይረካም። ባለቅኔው ፀጋዬ ገብረመድህን ይህንን አይነት ባሕርይ የሚገልፅ ግጥም አለው - “የተወጋ ቢረሳ፣ የወጋ አይረሳ” የሚል መልዕክት ያዘለ ግጥም ነው። በጥላቻ የተወረወረው ወጥመድ እየሰፋና እየተወሳሰበ ይቀጥላል። ወይም ደግሞ፣ ጥቃት፣ አፀፋ፣ የአፀፋ መልስ... እያለ፣ እየከረረና እየመረረ ይሄዳል። እቴጌ ሰርሲ፣ በዚህ በዚህ የሚስተካከላት የለም።
ታዲያ፣ እለት በእለት የምትዘረጋው ወጥመድና መረብ፣ ወንድሟን ዝም ለማሰኘት ብቻ አይደለም። ቅስሙን ሰብራ ለማንኮታኮትና አዋርዳ ለማሽቀንጠር ነው። ይህም አይበቃም። እስር፣ የግድያ ሴራ፣ የሞት ፍርድ... እየተከተለ ይመጣል።
እቴጌ ሰርሲ፣ እንደጠላትና ተቀናቃኝ የምታየው ወንድሟን ብቻ ሳይሆን፣ ነባር የንጉሥ አማካሪዎችንም ነው። ሌላም ይጨመርባታል። ልጇ ዘውድ በጫነ ማግስት፣ በለጋነቱ እድሜ ከምትበልጠው ሴት ጋር ተጋብቷል። ከተቀናቃኝ የመሳፍንት ቤተሰብ የተወለደችው ሚስት፣ ንጉሱን እንዳሻት ለማሾር ብላ ነው ያገባችው። ሃሳቧን ለማሳካትም ጊዜ አልወሰደባትም።
በዚህ የበገነችው እቴጌ ሰርሲ ላኒስተር፣  ተቀናቃኞቿን ሁሉ ለማጥፋት ዘዴ ስታውጠነጥን ነው የምትውለው፤ የምታድረው። እንደሌላው ጊዜ፣ ሁነኛ ዘዴ አገኘች። ከሌላው ጊዜም ይበልጣል እንጂ። ተቀናብሮ የተዘጋጀና ያለቀለት ዘዴ ነው ያገኘቸው። ከሷ የሚጠበቀው፣ የመወጠሪያ ገመድ አንድ ሁለቴ ሳብ ሳብ ማድረግ ብቻ ነው። መወጠሪያው ገመድ፣ የአጎቷ ልጅ ነው። ሁሌም ታዛዧ ነው፤ ... ሁሌም ታዛዧ ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን፣ አይታው አታውቅም።
የአጎቷ ልጅ፣ የሃይማኖት ቡድን ውስጥ በአባል እንደገባ መች አወቀች? ስታየው፣ ሌላ ሰው ሆኗል። እንደባህታዊ ነው የለበሰው። አነጋገሩም እንደድሮው አይደለም። ሁለመናው ተለውጧል። በጭፍን የሃይማኖት እምነት ተነክሯል። ከዚያም አልፏል እንጂ። ጭፍንነትን የሚያስተጋባ ሰባኪ ሆኗል (አክራሪ)። እሱና መሰሎቹ፣ “አገሬው ዌስትሮስ በሙሉ፣ በተለይም ዋና ከተማዋ ኪንግስ ላንዲንግ፣ በሃጥያተኞች ረክሳለች” በማለት ዘመቻ ጀምረዋል። ታዲያ ስብከት ብቻ አይደለም።
ሰው ሁሉ ስብከታቸውን ሰምቶ በጭፍን ቢያምንላቸውና ተከታይ ቢሆንላቸው እንኳ አያረካቸውም። የእያንዳንዱን ሰው አኗኗር ለመቆጣጠር ነው የሚመኙት - ለማዘዝ፣ ለማስፈራራትና ለማስገደድ። ሃብታምም ይሁን ድሃ፣ ገበሬም ይሁን ምሁር፣ ግንበኛም ይሁን ይሁን የመሳፍንት ዘር፣ የሃይማኖት ትዕዛዛትን የሚጥስ አንድም ሰው መኖር እንደሌለበት ይሰብካሉ። ሁሉም ሰው፣ ወደደም ጠላም፣ የሃይማኖት ትዕዛዛትን መፈፀም አለበት። በሌላ አነጋገር አመፀኛ አክራሪ ሆነዋል - ጉልበትንና ሃይማኖትን በማቀላቀል።
በእርግጥ፣ የተወሰኑ ሚስኪን ሰዎችንና አለኝታ ቢስ ሴተኛ አዳሪዎችን ከማሸማቀቅና ከመረበሽ ያለፈ ነገር ለማድረግ አቅም የላቸውም። ገና ብዙ ተከታይ አላገኙም። እንደተለመደው፣ “የምር ሃይማኖተኛ ናቸው” በሚል ብዙ ሰው ያደንቃቸዋል። በተግባር ግን፣ ዓለማዊ ኑሮውን ትቶ በማያፈናፍኑ ጭፍን የሃይማኖት ትዕዛዛት ለመታፈን የሚፈልግና እነሱን ለመቀላቀል የሚጎርፍ ብዙ ሰው የለም።
አብዛኛው ሰው “ሃይማኖተኞቹ”ን ቢያደንቅም፤ ‘በሆታ’ እየደገፈ አይቀላቀላቸውም። ሕዝቡን በሙሉ በጉልበት ለማስገደድ ቢሞክሩስ? አያዋጣቸውም። መንግስት ያለበት አገር ነው። መንግስትን ለመፈታተን ደግሞ፣ አቅማቸው አይፈቅድም። በአንዳች ተዓምር አቅም ማግኘት አይችሉም። አቅም የሚያገኙበት እድል የለም ማለት ግን አይደለም። ለዚያውም፣ ሳይወጡ ሳይወርዱ በቀላሉ አቅም የሚያገኙበት እድል ቢፈጠርላቸውስ? ለዚያውም፣ ራሱ መንግስት እድል ቢፈጥርላቸውስ? ለዚያውም ራሷ ንግስቲቱ!
እቴጌ ሰርሲ ላኒስተር፣ ተቀናቃኞቿን ለማጥፋት የሚጠቅማት ከሆነ፣ ለዓመፀኞቹ አክራሪዎች የተወሰነ ስልጣን ልትሰጣቸው ትችላለች። ብዙ ስልጣን አትሰጣቸውም። ትንሽ ብቻ። ከጎን በኩል ሚጢጢ መንግስታዊ ሃይማኖት እንደመፍጠር ማለት ነው - ከመንግስት ድጋፍ የሚያገኝ ሃይማኖት። “ያኛውን ወይም ይሄኛውን የሃይማኖት ትዕዛዝ ጥሰሃል” እያሉ የማሰርና የመፍረድ ስልጣን እንዲኖራቸው ማድረግ አያቅታትም። ተቀናቃኞቿ፣ “ዝሙት ፈፅማችኋል”፣ “ሃጥያትን በዝምታ አልፋችኋል” ተብለው ሲወነጀሉ፣ ሲታሰሩ፣ ሲዋረዱ... እየታያት በምኞት ብታሰላስል አልተሳሳተችም።
“ሃይማኖተኞቹ እኔ ላይ ቢዞሩብኝስ?” ብላ የምታስብበት ምክንያት ለጊዜው አልታያትም። ንግስት ናት። የንጉሡ እናትና ቀኝ እጅ ናት። ማን ይነካታል? በእርግጥ፣ ተቀናቃኞቿም ‘ማንም አይነካንም’ ብለው የሚያስቡ አውራ ሰዎች ናቸው። ሃይማኖተኞቹ የሰርሲን ተቀናቃኞች የማጥቃት ስልጣን ካገኙ፣ በዚያው ያቆማሉ? እንዲያም ሆኖ፣ ሰርሲ ፈፅሞ ስጋት አልገባትም።
አንደኛ፣ ለሃይማኖተኞቹ ባለውለታቸው ናት፤ ስልጣን እንዲያገኙ አድርጋለች። ... ግን፣ “የሰጠችንን ስልጣን መልሳ ልትነጥቀን ትችላለች” በሚል፣ እንደዋና ጠላት ቢያዩዋትስ? ከመንግስታዊ ሃይማኖት ወደ ሃይማኖታዊ መንግስት መሻገር ቢያምራቸውስ? የማይሆን ነገር ነው! ይሆናል?
ሁለተኛ፤ ታዛዧ የነበረው የአጎቷ ልጅ በሃይማኖተኞቹ ቡድን ውስጥ ቁልፍ ቦታ መያዙ፣ ሊጠቅማት ይችላል። የቅርብ ዘመዷና በቅርብ የምታውቀው የአጎቷ ልጅ፣ ለጥቃት አጋልጦ አይሰጣትም። አይደለም? ...ግን፣ የቅርበቱ ያህል፣ ሃጥያተኛ ተብላ እንድትወገዝ የሚያደርጉ ብዙ ሚስጥሮቿን ያውቃል። በዚያ ላይ፣ በዝምድና የመቧደን ዘረኝነት፣ ገለጥ ተደርጎ ሲታይ ባዶ ነው። ዘረኝነት፣ ኦና ሰብዕናን ለመሙላት የሚያገለግል ባዶ ውሸት መሆኑን እንዴት ዘነጋችው? ዙሪያውንና ራሷን ብትመለከት በቂ ነው። ተቀናቃኞቿን የምታሳድዳቸው፣ የሩቅ ሰዎች ስለሆኑ አይደለም። ወንድሟን ጭምር ለማጥፋት የምታሴረው፣ በዘርና በዝምድና ስለተራራቁ ነው እንዴ? እና በዝምድና ትስስርና በአጎቷ ልጅ ብትተማመን ያዋጣታል? ... ቢሆኖም አላሳሰባትም።
ሦስተኛ፣ ከተቀናቃኞቿ ከተገላገለች በኋላ፣ አመፀኞቹ አክራሪዎች ከልክ እንዳያልፉና ጭፍን እምነታቸውን እንዲያለዝቡ በምክንያታዊ ውይይት ልታሳምናቸው ትችል ይሆናል። ...ግን ደግሞ፣ ከመነሻው ተቀናቃኞቿን እንዲያጠፉላት የመረጠቻቸው ለምን ሆነና? ከጭፍን እምነት የማይነቃነቁና ለምክንያታዊ ውይይት ቅንጣት ቦታ የማይሰጡ በመሆናቸው አይደል? ቢሆንም... አላስጨነቃትም።
“What goes around comes around” የሚለውን የብልሆች አባባል አታውቀውም፤ ወይም ደንታ አልሰጣትም። ወደ ሌሎች አቅጣጫ “ጃስ” ብላ የለቀቀችው አውሬ፣ ወደራሷ አቅጣጫ እየተንደረደረ ቢመጣ... ማስቆሚያ ዘዴ አላት? አሁን የሚያሳስባት፣ ይሄ ሳይሆን፣ የስልጣንና የፖለቲካ ቁማር ነው። በዚሁ ቁማር ውስጥ፣ የሃይማኖት አክራሪነት የመጫወቻ ካርድ እንዲሆንላት ትፈልጋለች። ብዙም ሳይቆይ መልሶ መጫወቻ እንዳያደርጋት አስተማማኝ መከላከያ ይኖራት ይሆን? ለቁጥር የሚታክቱ የአለማችን አሳዛኝ ታሪካዊ ጥፋቶች የተለኮሱት፣ እንደ እቴጌ ሰርሲ በምኞት የሰከሩ ሰዎች በሚፈፅሙት ስህተት ሰበብ ነው። እያንዳንዱ ሰበብ የራሱን መዘዝ ጎትቶ ያመጣልና።
ይሄ የታሪክ ሰንሰለት፣ በዘንድሮው የጌም ኦፍ ትሮንስ ተከታታይ ድራማ ውስጥ ጎልተው ከሚታዩ የታሪክ ትልሞች አንዱ ነው - በዌስትሮስ ምድር፣ የዋና ከተማዋ የኪንግስ ላንዲንግ ትልም ልንለው እንችላለን።

2. የመስዋዕት አምልኮ (የሰው ሕይወት=የማገዶ እንጨት)
ከወደ ሰሜን በምትገኘው በዊንተርፌል ዙሪያ ሁለት ጎራዎች የሚያካሂዱት ትንቅንቅ ላይ ያጠነጠነ ሌላ ታሪክ አለ። ስልጣን ለመያዝ ወደ መዲናዋ ለመዝመት ያቀዱት ሁለቱ ጎራዎች፣ በቅድሚያ አንዱ ሌላውን በማጥፋት ሰፊውን የሰሜን ግዛት ለመቆጣጠር ይጨፋጨፋሉ።
በአንድ በኩል፣ የጭካኔ ባህርይ የተጠናወተው የሩስ ቦልተን ጎራ አለ። “ሰው ሰጥ ለጥ ብሎ ስርዓት የሚይዘው፣ መቀጣጫ ሲያይ ነው” በሚል ሰበብ የጭካኔ ባሕርይ ተላብሰዋል። እንደ ክፉ አውሬ ያደርጋቸዋል ቢባል ይቀላል። የአባትዬው ከሩሶ ቦልተን ጭካኔ ያነሰ ይመስል፣ የልጅዬው የራምሰስ ይብሳል።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ የመስዋዕትነት አምልኮ የተጠናወተው፣ የስታነስ ባራቲያን ጎራ አለ። “አገሬውን በስርዓት የማስተዳደር ታሪካዊ ሃላፊነት ተጭኖብኛል” ብሎ የሚያስበው ስታነስ፣ በዚህ ጉዳይ ላይ፣ የእያንዳንዱ ሰው ሕይወት ከስንጥር የበለጠ ዋጋ እንደሌለው ያምናል። “ሕይወትህ፣ ከማገዶ እንጨት የተሻለ ዋጋ የለውም” በሚል እምነት እንደመመራት ነው። እናም እያንዳንዱ ሰው ራሱን ለመስዋዕትነት ማቅረብ ግዴታው ነው። የአገራችን የ60ዎቹ ዓ.ም ሶሻሊስቶች ሲያስተጋቡት ከነበረው መዝሙር ብዙም አይለይም።
“ይህ ነው ምኞቴ እኔ በሕይወቴ
ከራሴ በፊት ለኢትዮጵያ እናቴ”
ታዲያ፣ አዳሜ እንዲህ በመስዋዕትነት የሚያምን ቢሆንም፣ ራሱን እንደ በግ ለእርድ እንደ እንጨት ለማገዶ በፈቃደኝነት የሚሰጥ ቂላቂልና እብድ ሰው ብዙ አይገኝም። “መስዋዕት ማለት የራስህን አላማ ለማሳካትና ሕይወትህን ለማሻሻል፣ ከባባድ ችግሮችንም ተቋቁመህ የአቅምህን ሁሉ መጣር ማለት ነው” ብሎ ነገሩን ለማለሳለስና ራሱን ለማታለል የሚሞክር አይጠፋም። ግን ዋጋ የለውም።
በስታነስ አገር፣ መስዋዕት ማለት መስዋዕት ነው። “የራስህ አላማ ገደል ይግባ፤ ሕይወትህ ነድዶ ይጥፋ” ... በቃ፣ እንደ ማገዶ እንጨት። ይሄ ነው መስዋዕትነት። ነገርዮው፣ እንዲህ የሕይወትና የሞት ጉዳይ ቢሆንም፣ አዳሜ ቆም ብሎ የመስዋዕትነት አምልኮውን በቅጡ ለመመርመርና ክፉ እምነት መሆኑን ለመገንዘብ አይፈልግም። መስዋዕትን እያዳነቀ በሕይወት ለመቀጠል ይመኛል (የስቃይ አምልኮ፤ ከጤናማ ሰው የሚጠበቅ ባይሆንም)።
ሁሉም ሰው፣ ሙሉ ለሙሉ ጤና አጥቷል ማለት ግን አይደለም። እምነቱን ተከትሎ በቁሙ ከእንጨት መሃል ገብቶ መቃጠልን አይፈልግም - እንደማንኛውም ጤናማ ሰው። መቼም ቢሆን፣ የመስዋዕት ፅዋ የኔ ተራ ይሆናል ብሎ አያስብም። ሌሎች በመስዋዕት እሳት ሲቃጠሉ ግን፣ ተመልካችና አዳናቂ ይሆናል።
በእርግጥም፣ መነሻው ላይ የእሳት እራት የሚሆኑት፣ በጠላትነት ወይም በተቀናቃኝነት የተፈረጁ ሰዎች ናቸው - እንዲህ አይነት ሰበብ ተገኝቶማ ማን ይምራቸዋል? ግን በነሱ አያበቃም። የመስዋዕት ቃጠሎን ሁልጊዜ  እያዳነቁ፣ ሁልጊዜ ከእሳት ማምለጥ እንዴት ይቻላል?
ቢሆንም፣ ስታነስ ባራትያን ከሌላው ሰው የተለየ ያን ያህል “ክፉት” አይታይበትም። ሰዎችን አቃጥሎ የመጨረስ ምኞት የለውም። አዎ፣ ብዙ ወንጀል፣ ብዙ ጥፋት ሰርቷል። የአገርንና የትውልድን ሃላፊነት መሸከም እጣ ፋንታዬ ነው በሚል ሰበብ የሰራቸውን ጥፋቶች፣ እንደገና ወደ ነበሩት መመለስ ቢችል የሚመኝበት ጊዜ አለ።
ሌላ ሌላውን ነገር ሁሉ ትቶ፣ ከሚስቱና ከአንዲት ልጁ ጋርበሰላም የቤተሰብ ሕይወቱን በፍቅር የመኖር ምኞትም ያብሰለስለዋል። ቅሬታ የለውም ማለት አይደለም። እንደሌሎቹ የመሣፍንት ቤተሰቦች፣ ወንድ ልጅ አለመውለዱ ያንገበግበዋል። አንዳንዴም፣ ሚስቱን ጥፋተኛ አድርጎ እያየ የጥላቻ ስሜት ሽው ይልበታል።
ሴት ልጁ እንደሌሎች ልዕልቶች አለመሆኗም ያሳርረዋል። የግራ ፊቷ፣ በበሽታ ምክንያት የዝሆን ቆዳ መስሏል። እንዲያም ሆኖ፣ ነፍሷ ንፁህ ነው። ገና ሕፃን ብትሆንም፣ ከቅንነትዋ ጋር ብሩህ አእምሮዋ የደስ ደስ ገፅታን ሰጥቷታል። የምትወደድ ልጅ ናት። ከሁሉም በላይ ደግሞ አባቷ ስታነስ ባራትያን ይወዳታል። እንዲያውም ከሷ በላይ በሕይወቱ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ሌላ ነገር እንደሌለ ይሰማዋል - ብዙውን ጊዜ (ሁሌ ባይሆንም)።
ከዚህ ውጪ፣ ሌላው ሌላው ሁሉ ሸክም ነው። ይሄ አገርን የመምራት ጉዳይ፣ በራሱ ፈቃድ መርጦ የተቀበለው ነገር ሳይሆን፣ እጣፈንታው ሆኖ በግድ የተጫነበት ሃላፊነት ነው - ከአባት፣ ከአያት የተወረሰ። አጠገቡ የሚገኙ የሰሜን ተቀናቃኞቹን የማንበርከክ፣ ከዚያም ወደ ዋና ከተማዋ ወደ ኪንግስ ላንዲንግ ዘምቶ ስልጣን የመያዝና አገሬውን የማስተዳደር ሃላፊነት ተጥሎበታል። ለዚህ ነው፣ በርካታ የቃጠሎ መስዋዕቶችን መገበር ግዴታ የሆነበት...
ስታነስ ባራትያን ይህን ሁሉ የሚያወራው፣ ራሱን ለማታለል እንጂ፣ በግዴታ ሸክም የጫነበት ሰው የለም። ሰዎችን ለቃጠሎ መስዋዕት እንዲማግድ ያስገደደው ሃይል የለም። “ሃላፊነት እጣፈንታዬ ነው። መስዋዕት የግድ ነው። ሰዎች ሳይማገዱ፣ ያለ መስዋዕትነት ጥሩ ውጤት አይገኝም” ብሎ የሚያምነው በራሱ ምርጫ ነው።
ቢሆንም፣ ሰዎች በእሳት ሲነዱ ማየት ያስደስተዋል ማለት አይደለም። እንደ ሩስ ቦልተንና እንደ ራምሰስ የጭካኔ አባዜ አልተጠናወተውም - ስታነስ።
እንዲያውም፣ ስለ ቃጠሎ መስዋዕት የማያስብበት ጊዜ ቶሎ እንዲመጣ ይመኛል። የእስከዛሬው ይበቃል። የሰሜን ተቀናቃኞቹ ላይ ለመዝመት ተዘጋጅቷል። በአንድ ውጊያ ያሸንፍና ወደ ዋና ከተማይቱ ይገሰግሳል። በቃ። ግን፣ የጦርነት ዘመቻ እንደ አፍ አይቀልም። የሽምቅ ጥቃት ያጋጥማል። ጋራ ሸንተረሩ ሁሉ በበረዶ ግግር ተሸፍኖ አላንቀሳቅ ይላል። ቀን አልፎ ቀን ሲተካ፣ ስንቅ የተመናመነበት ጦር፣ በቆፈን እየተኮራመተ በበሽታ ይዳከማል...።
ይሄኛውን ችግር ለመፍታት፣ ያኛውን ውጥን ለማቃናት፣ ለዚህኛውም ለዚያኛውም፣ ቁልፉ መላ የመስዋዕት ቃጠሎ ብቻ ነው። የማይወደዱ፣ የተናቁና ከንቱ ሰዎችን በማቃጠል የተጀመረው የመስዋዕት አምልኮ፣ ትንሽ ቆይቶ ዜማው ይቀየራል። “ይሄ ምኑ እንደመስዋዕት ይቆጠራል? የመስዋዕት ዋጋ ከፍ የሚለው፣ የሚወደዱ፣ የሚከበሩና ደህና ሰዎች ላይ ሲሆን ነው” ወደሚል ማምራቱ ይቀራል? በዚህ ከቀጠለስ መጨረሻው የት ነው? “እጅግ የምትወዳት አንድያ ልጅህን ለመስዋዕት ካላቀረብካት ድል አይቀናህም” ወደ ሚል ደረጃ ባይደርስ እንኳ፣ የመስዋእት ጥሪ ወደ ስታነስን ቤት አምርቶ በር ባያንኳኳ እንኳ፣ የእሳቱ ነበልባል ዙሪያውን መለብለቡ ይቀራል?
የጌም ኦፍ ትሮንስ ሁለተኛው የታሪክ ትልም በዚህ አቅጣጫ ነው እየከረረና እየመረረ የሚጓዘው። “እያንዳንዷ መንስኤ የራሷ ውጤት፣ እያንዳንዷ ሰበብ የራሳ መዘዝ አላት” የምንል ከሆነ፤ “ድራማው አይምሬ ነው” ልንለው እንችላለን።

3. በተወላጅነት እየተቧደኑ፣ ወደ እልቂት!
ሦስተኛው የታሪክ ትልም፣ የመጨረሻው ጠረፍ የዌስትሮስ ድንበር ላይ የሚካሄደው ግብግብ ነው። እንደ ተራራ ከገዘፈው የበረዶ ግንብ ባሻገር፣ ጦረኛነትና አረመኔነት የገነነባቸው መዓት ጎሳዎች አሉ። wildling ይሏቸዋል።
በርካታዎቹ የጎሳ መሪዎችና ጦረኞች፣ የበረዶ ግንቡን የማለፍ እድል ቢያገኙ፣ የዌስትሮስ ግዛቶችን ከላይ እስከ ታች ለመዝረፍና የቀረውን ለማውደም፣ ህዝቡን ሁሉ ለመግደል የሚመኙ ናቸው። ትንሽ እግራቸውን ለማስገባት በቻሉበት አጋጣሚ ሁሉ፣ በድንበር አካባቢ በደም የማይጨቀይ የዌስትሮስ ከተማና መንደር የለም።
“ሕፃን ሽማግሌ ሳይሉ የሚገድሉ አውሬዎች ናቸው። ዌስትሮስን ለመዝረፍና ለማጥፋት የሚፈልጉ አረመኔዎች!” በቃ፣ ከበረዶው ግንብ ባሻገር የሚኖር ሰው በሙሉ፣ (መዝረፍና መግደል የሚመኝም ሆነ የማይመኝ)በጅምላ “የአረመኔዎች ወገን” ተብሎ ይፈረጃል። እንደ ጆን ስኖው፣ “ሰዎችን በጅምላ ሳይሆን እንደየድርጊታቸውና ባሕርያቸው እንደመዝናቸው” የሚል አዝማሚያ የሚያሳይ ሰው ካለ፣ “ከሃዲ” ተብሎ ይፈረጃል። ዘረኝነት እንዲህ ነው።
ከድንበሩ ባሻገርም ተመሳሳይ የዘረኝነት ባህል ነግሷል - “የዌስትሮስ ሰው ሁሉ ክፉ ጠላታችን ነው” በሚል ፍረጃ።

የዌስትሮስን መጨረሻ - “ከሰበብ ወደ መዘዝ”።
የዌስትሮስ ምድር፣ እንዲህ በሦስቱም አቅጣጫዎች፣ በጥፋት አፋፍ ላይ የደረሰች አገር ናት። ከወዲያ ጫፍ፣ የሃይማኖት አክራሪነት ይቆሰቆሳል። ከመሃል የመስዋዕት መዝሙር ይስተጋባል። ከወዲህኛው ጫፍ የዘረኝነት ጥላቻ ይግለበለባል። የሞት መንጋ እየተግተለተለ፣ እልፍና እልፍ ሆኖ እየተመመ እየመጣ እንደሆነ ሲያዩ፣ አብዛኞቹ ሊጋፈጡት ይፈልጋሉ? ወይስ አይተው እንዳላዩ በመሆን፣ በጭፍን እምነት፣ በመስዋዕትነትና በዘረኝነት እብደት መጓዝን ይመርጣሉ?
የዘንድሮው የጌም ኦፍ ትሮንስ ተከታታይ ድራማ፣ ከእስከዛሬዎቹ ይበልጣል የምለው ከላይ ያቀረብኳቸው የታሪክ ትልሞች፣ ጥልቀት ባላቸው ቁልፍ ጭብጦች (ሃሳቦች) የተቃኙና በጥራት ነጥረው የተቀረፁ የታሪክ ሰንሰሎች ሆነው በመቅረባቸው ነው።

Published in ህብረተሰብ

ኢጣሊያ ምሥራቅ አፍሪካ ጠቅላይ ግዛት
የፕሮቶኮል መዝገብ ቁጥር 9325
አዲስ አበባ ግንቦት 24/1937 ዓ.ም.

ጥብቅ ምስጢር፡- ለጄኔራል ማሌቲ- ደብረ ብርሃን፣
ለክቡር ምክትል ገዥ ኤታማጆር- አዲስ አበባ፣
ለፖለቲካ ጉዳይ ዋና አዛዥ- አዲስ አበባ፣
ለጦር ፍርድ ቤት- አዲስ አበባ፣
ለካራቢኜራዎች ዋና አዛዥ- አዲስ አበባ፡፡
ቁጥር 26609- የደብረ ሊባኖስ ጉዳይ ሙሉ ሓላፊነቱ የእርስዎ እንደሆነ አረጋግጬያለሁ፡፡ የደብረ ሊባኖስ ገዳም መነኮሳትና ዲያቆናት ሁሉም አንድ ሣይቀር በጥይት እንድትፈጇቸው አዝዣለሁ፡፡ ትእዛዝህን በአስቸኳይ አስፈፅሜያለሁ በሚል ቃል እንድታረጋግጥልኝ ይሁን!
ማርሻል ሩዶልፎ ግራዚያኒ


ክፍል-፩
ለዛሬው ጽሑፌ መነሻ የሆኑኝ ሁለት ዐበይት ምክንያቶች ናቸው፡፡ የመጀመሪያው በዚህ ዓመት በአሜሪካዊው ምሁር በፕ/ር ኢያን ካምፔል፤ ‹‹The Massacre at Debre Libanos Ethiopia 1937:- The Story of One of Fascism’s Most Shocking Atrocities›› በሚል ርእስ የተጻፈው መጽሐፍ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የኒው ዮርክ ታይምስ ከሁለት ሳምንት በፊት የአርመን ኦርቶዶክስ ቤ/ን ከመቶ ዓመት በፊት ቱርካውያን በአርመን ክርስቲያኖችና አብያተ ክርስቲያናት ላይ ላደረሱት ግፍና መከራ የአርመን ቤተክርስቲያን መሪና መንፈሳዊ አባት የሆኑት አቡነ አራህም I የቱርክ መንግሥት ለቤተ ክርስቲያኒቱ ተገቢውን ካሣ እንዲከፍል የጠየቁበትና ያሳሰቡበት ሰበር ዜና ነው፡፡
 ከሰሞኑ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ላይ ሰፊ ምርምርና ጥናት በማድረግ የሚታወቁት አሜሪካዊው ምሁር ፕ/ር ኢያን ካምፔል፤ የፋሽስት መንግሥት በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በተለይም ደግሞ በደብረ ሊባኖስ ገዳም መነኮሳትና አገልጋዮች ላይ ያደረሰውን ዘግናኝ ጭፍጨፋና እልቂት፣ መከራና ሥቃይ በተመለከተ የሚተርከውን መጽሐፍ በቁጭትና በኀዘን ውስጥ ሆኜ ነው ያነበብኩት፡፡
መጽሐፉ የፋሽስት መንግሥትን የጭካኔና የአውሬነት ጥግ በሥዕላዊ ቃላት የሚከስት፣ የሚገልጽ ድንቅ ሥራ ነው ብል እምብዛም ያጋነንኩ አይመስለኝም፡፡ በፈጣሪ አምሳል የተፈጠረውን መሰሉ የሆነውን የሰው ልጅን ለሚወድና ለሚያከብር፣ ሰብአዊነት፣ ፍቅርና ርኅራኄ ምን ማለት መሆኑን ለተረዳ ሰው ለሆነ ሰው ሁሉ ፋሽስት በሰው ልጆች፣ በወገኖቻችን ላይ ያደረሰው ግፍና ጭካኔ፣ ጭፍጨፋና እልቂት ልብን በኀዘን ጦር የሚወጋ፣ ሰው የመሆን ታላቅ ክብርን በትልቅ ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው፡፡
እኚህ ምሁር አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስግዶም የተባሉ ወጣት ኤርትራውያን በፋሽስቱ ጄኔራል በማርሻል ሩዶልፎ ግራዚያኒ ላይ በቀድሞው ገነት ልዑል በአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ካደረጉት የግድያ ሙከራ ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ላይ የታወጀው ግድያና ጭፍጨፋ፣ እልቂትና ፍጅት ወደ ደብረ ሊባኖስም ዘልቆ በርካታ መነኮሳት፣ ካህናት፣ ዲያቆናትና ምእመናን በግፍ ማለቃቸውን፣ ተጨባጭ ከሆኑ መረጃዎች፣ ታሪካዊ ሰነዶችና ፎቶግራፎች ጋር አጠናክረው ፋሽስት በገዳሙ ላይ ያደረሰውን ውድመትና እልቂት፣ ኢ-ሰብአዊ የሆነ ግፍና ጭፍጨፋ በሚገባ ተርከውታል፡፡
ምሁሩ በጊዜው ከዚያ አሰቃቂ እልቂት የተረፉትን አባቶች ቃለ መጠይቅ በማድረግ፣ በደብረ ሊባኖስ ገዳም በሚገኙ መነኮሳትና አገልጋዮች ላይ ፋሽስቱ ሞሶሎኒ ለጦር ባልደረቦቹ ያስተላለፈውን የግድያ ዕርምጃ የሚያረጋግጡ የቴሌግራም መልእክቶችንና ምስጢራዊ የሆኑ ሰነዶችን በመመርመር፣ ለበርካታ ዓመታት ጥናት ያደረጉበትን ይህን መጽሐፋቸውን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ ለንባብ አብቅቶታል፡፡
ኢትዮጵያም ሆነ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በፋሽስት ኢጣሊያ የደረሰባቸውን ግፍና መከራ፣ እልቂትና ጭፍጨፋ መላው ዓለም ያውቀው ዘንድ ይህን መጽሐፍ ያበረከቱልን ፕ/ር ኢያን ካምፔል ባለውለታችን ናቸውና ልናመስግናቸውና ለሥራቸውም የሚገባውን እውቅና ልንሰጣቸው ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስም ለእኚህ ምሁር የሚገባውን ክብርና ዕውቅናም ቢሰጣቸው መልካምና ተገቢም ይመስለኛል፡፡
በዛሬው ጽሑፌ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በፋሽስት ስለደረሰባት ግፍና መከራ፣ በአገልጋዮቿና በመእምናኖቿ ላይ ስለደረሰው አሰቃቂ ጭፍጨፋና እልቂት የኢጣሊያን መንግሥት ይቅርታ በመጠየቅ ተገቢውን ካሣ ሊከፍላት ይገባል!›› ያልኩበትን ምክንያት ከታሪክ ድርሳናትና መዛግብቶች በመፈተሽ በጥቂቱ ለማብራራት ልሞክር፡፡
የኢትዮጵያ ቤ/ን ለኢትዮጵያና ለሕዝቦቿ ስለ ሰው ልጆች ከፈጣሪው ስለ ተቸረው ነጻነት ከመናገርና ከማስተማር ባሻገርም ነፍሳቸውን ለአገራቸውና ለሕዝባቸው ነጻነት ክቡር መሥዋዕት አድርገው ያቀረቡ ፍቅርንና እውነትን፣ የነጻነትን ክብርና ልእልና በደማቸው ጽፈው የተረኩና ለዚህ ክፉና ጨካኝ ዓለም በተግባር አሣይተው ያለፉ አባቶች ያለፉባትና ያሉባት ሐዋርያዊት ቤ/ን ናት፡፡
እንደ ሰማዕታቱ አቡነ ጴጥሮስና አቡነ ሚካኤል ያሉ እውነተኛ፣ ኢትዮጵያዊ መንፈሳዊ አባቶችና የወንጌል አርበኞች “ቤተ ክርስቲያናችን በሮማ ካቶሊክ ሥር አታድርም፣ በሕይወት ቆመን እያለን ቤተ ክርስቲያናችንና ሕዝባችንን ቅኝ ለማድረግ የቋመጣችሁለት ይህ የዘመናት ሕልማችሁ ዕውን አይሆንም፤ አገራችንም ሆነ ሕዝባችን ለፈጣሪ እንጂ ለእናንተ ፈጽሞ አይገዛም፣ ከፈጣሪ የተቸረንን የአገራችንን፣ የቤተ ክርስቲያናችንንና የሕዝባችንን ነጻነትና ልዑላዓዊነትም ለእናንተ ለጨካኞችና ለአውሬዎች አሳልፈን አንሰጥም” በማለታቸው ነበር- እምነታቸውን፣ ቃላቸውን እንደጠበቁ፣ እንዳከበሩ በፋሽሽት መትረየስ በአደባባይ ተደብድበው እንዲገደሉ፣ እንዲረሸኑ የተደረጉት፡፡
የጨካኞቹና የአውሬዎቹ የፋሽስት የሞት አበጋዞች ማስፈራራትና መደለያ መንፈሳዊ ጽናታቸውን ፈጽሞ ሳይበግረው ሞትን በፍቅር ድል ነሥተው ዘላለማዊነት የተጎናጸፉ እነዚህ አባቶቻችን፤ ‹‹ኢትዮጵያዬ ብረሳሽ ቀኜ ትርሣኝ፣ ምላሴ ከትናጋዬ ይጣበቅ!›› በሚል ጽኑ የመኻላ ቃል ታስረው፣ ‹‹እግዝእትነ ማርያም ስሚዕ ኀዘና ወብካያ ለአገሪትነ ኢትዮጵያ!›› ብለው እንባቸውን በጽድቅ ለሚፈርድ አምላክ ወደ ሰማይ ረጭተው፣ በጸሎታቸው ተማፅነው፣ ቃል ኪዳናቸውን ሣያረክሱ፣ ቃላቸውን ሳያጥፉ፣ እትብታቸው የተቀበረባትን እናት ምድራቸውን በደማቸው ቀድሰውና በመስቀላቸው ባርከው፣ በእንባቸውና በደማቸው ነጻነታቸውን አውጀው ወደሚናፍቁት አምላካቸው በሰማዕትነት በክብር የሄዱት፡፡
የኢትዮጵያ ታላቅ ባለውለታ የነበሩትና የኢጣሊያን ፋሽስት ጭካኔና ግፍ ለዓለም ሁሉ በማጋለጥ ከኢትዮጵያውያን ጎን የቆሙት ሲሊቪያ ፓንክረስት፤ የፋሽስቱ መሪ ቤኒቶ ሞሶሊኒ በሃይማኖት አባቶች ላይ እየተወሰደ ያለው ዕርምጃ ሌሎች ኢትዮጵያውያንን ሊያሸማቅቅ እንደሚችልና ጭፍጨፋውም ውጤታማ እንደሆነ በወቅቱ ለምስራቅ አፍሪካ ለቅኝ ግዛት ሚ/ሩ ለግራዚያኒ ያስተላለፈውን ምስጢራዊ የቴሌግራም መልእክት Ethiopia and Eritrea በሚለው መጽሐፋቸው እንዲህ ጠቅሰውታል፡-
… The execution of Abune Petros, one of the four Ethiopian bishops, has terrified the leaders and the public. The work of repression against armed groups dispersed in the forest continues. All prisoners have been shot. Inexorable reprisals have been effected against the populations guilty, if not complicity, at least of lack of favourable attitude. A telegram of March 1, 1937.
‹‹በአቡነ ጴጥሮስ ላይ የተወሰደው የግድያ ዕርምጃ ብዙዎችን እንዲፈሩና እንዲሸማቀቁ አድርጓል፤ ይህ ዓይነቱ እርምጃ ለኢጣሊያን እንዳይገዛ ሕዝቡን በሚያነሣሡና በዱር በገደል በአርበኝነት በተሰማሩት ፋኖዎችም ላይ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል . . . ፡፡››
የታሪክ ድርሳናትን ስንፈትሽ በተለያዩ ጊዜያት ኢትዮጵያን ቅኝ ለመያዝ፣ ሕዝቦቿን ለመግዛት የመጡ አውሮጳውያን ወራሪዎችና የአረብ ተስፋፊዎች ሁሉ ቤተ ክርስቲያኒቱ ቀዳሚ ዒላማ ልትሆን የቻለችባቸው ራሱን የቻለ ምክንያት አለው።  ይኸውም ቤ/ቱ በኢትዮጵያ ነጻነትና ልዑላዊነት ላይ ያላት ጠንካራና የማይለወጥ፣ የማያወላውል ጽኑ አቋም ነው፡፡ ዳንኤል ሮፕስ የተባለ ፈረንሳዊ ጋዜጠኛ እ.ኤ.አ. ፲፱፻፷፫ ‹‹አክሌዥያ›› በሚባል በፓሪስ ከተማ ለሚታተም ጋዜጣ፡- ‹‹የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን ታውቃላችሁን?›› በሚል ርዕስ ባሰፈረው ሰፊ ሐተታም እንዲህ ሲል ምስክርነቱን ሰጥቶ ነበር፡-
ኢትዮጵያ ወራሪዎች ምድርዋን በግፍ የያዙባት መሆኑን ታሪክ ያወሳል፤ ነገር ግን ሃይማኖቷ ኃይሏና የእንቅስቃሴዋ መሳሪያ ሆኖ በመገኘቱ ነጻነቷን መልሳ አግኝታለች፡፡ በማዕከላዊው ክፍለ ዘመን ‹‹የካህን የዮሐንስ ግዛት›› በአረመኔው ዓለም ተከቦ የክርስቲያን ምሽግ ሆነዋል እየተባለ ስለ ኢትዮጵያ ይነገር የነበረው ሁሉ ፍጹም ልበ-ወለድ ታሪክ አይደለም፡፡ ከሁለት ሺሕ ሜትር በላይ ከፍታ ያለውን ደጋማና ለምለም መሬት ቁልቁል የሚያዩት ቀይ፣ ጥቁርና ሰርጥነት ያላቸው የእሳተ ገሞራ ውጤት ባሕርይ ያላቸው ጠረጴዛ መሰል ተራራዎች የጊዜን ውሽንፍር እንዳሳለፉትና የባሕር ዓሣም ሳይበገርና ሳይላላ ማዕበሉን እንደሚያሳልፍ ክርስቲያኒቷ ኢትዮጵያም በታሪክ ውስጥ ጠንካራ ስፍራዋን ይዛና አስከብራ ቆይታለች …፡፡ በማለት ጽፏል፡፡
ይህን ቤተ ክርስቲያኒቱ በኢትዮጵያ ልዑላዊነትና በሕዝቦቿ ነጻነት ላይ ያላትን የማያወላውል ጽኑ አቋም በሚገባ የሚያውቁ አውሮጳውያን ቅኝ ገዢዎች፣ ወራሪዎችና ተስፋፊዎችም በተለያዩ ዘመናት ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማፍረስና ቢቻላቸውም በራሳቸው ግዛትና ቁጥጥር ሥር ለማድረግ ያልቆፈሩት ጉድጓድ፣ ያልወጡት ተራራ የለም ማለት ይቀላል። አልተሳካላቸውም እንጂ፤ ይህ ሙከራቸው ደግሞ መልኩንና ይዘቱን ቀይሮ እስካሁንም ድረስ የዘለቀ ነው ማለትም ይቻላል፡፡
የኢትዮጵያ ቤ/ን በውጭ አገራት ወራሪዎችና ቅኝ ገዢዎች ዘንድ ጥርሳቸው እንዲነኩስባትና በተለያዩ ዘመናት ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ያጋጠማቸውን ወረራ፣ የቅኝ ግዛት መስፋፋት በማውገዝና በመቋቋም ረገድ ያደረገችውን ተጋድሎና የከፈለችውን ክቡር መሥዋዕትነት ከታሪክ ድርሳናትና መዛግብት እየፈተሽኩ ሁሉንም ለመተረክ የዚህ ጋዜጣ ገጽም ሆነ ጊዜው አይፈቅድልኝም። ግና ወደተነሣሁበት መደምደሚያ የሚያደርሰኝንና በኢትዮጵያ የዘመናዊ የታሪክ ዘመናት በቅርብ ዓመታት የተከሰቱትን የአውሮጳውያን ወረራዎችና ቅኝ ገዢ ተስፋፊዎች ሕልማቸውን በማምከን ቤተ ክርስቲያኒቱ የነበራትን ተሣትፎና ዐቢይ ሚና ብቻ በመዳሰስ የዛሬውን የመጀመሪያ ክፍል መጣጥፌን ልቋጭ፡፡
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ክብሯንና ዝናዋን በዓለም አቀፍ እንዲናኝ ካደረጉት ታሪካዊ ክስተቶች መካከል የዐድዋው ድል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ከጦርነት ዘመቻው ዝግጅትና፣ ከዘመቻውና ድሉ ድረስ ቤተ ክርስቲያኒቱ ያልነበረችበት፣ ያልተሳተፈችበት አጋጣሚ አልነበረም፡፡ ይህ ደግሞ ትናንትና በአገር ወሰንና ድንበር ተከልሎ የሆነ ብቻ አይደለም፡፡ ከታሪክ እንደምንማረው ለአብነት ያህል ለመጥቀስም አክሱማዊው ንጉሥ ዐፄ ካሌብ ከአንድ ሺ አምስት ዓመታት በፊት በየመን ግፍ፣ መከራና ስደት ካጸኑባቸው ሰዎች ነጻ ሊያወጣቸው በመቶ የሚቆጠሩ ጦር መርከቦችንና ወታደሮችን ይዞ በየመን ያሉ ክርስቲያኖችን ለመታደግ ዘምቶ እንደነበር ታሪካችን ይነግረናል፡፡
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለሰው ልጆች ኹሉ ከፈጣሪ በተሰጠ ነጻነት፣ በእውነት፣ በፍትሕ ላይ ያላት ጽኑ የሆነ አቋም ስለ ነጻነታቸው፣ ስለ ፍትሕና ስለ ሰው ልጆች እኩልነት በሚታገሉና በሚጋደሉ የዓለም ሕዝቦች ሁሉ ዘንድ የተሰማ፣ ትልቅ ክብርና ዝና ያለው ነው፡፡ በተለይም ደግሞ አውሮጳውያን ቅኝ ገዢዎችንና ተስፋፊዎችን በእጅጉ ያደናገጠውና ያሳፈረው በዓድዋው ጦርነትና አንጸባራቂ ድል ላይ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከዘመቻው ጀምሮ እስከ ጦር ግንባር ድረስ የነበራትን ተሣትፎ ከአፍሪካ እስከ ላቲን አሜሪካ፣ ካረቢያና ጃሜይካና ደቡብ አፍሪካ ድረስ የተሰማና ጥቁር ሕዝቦችን ያኮራ ነበር፡፡
ይህ የቤተ ክርስቲያኒቱ ክብርና ዝና በመላው አፍሪካ፣ አሜሪካና አውሮጳ ድረስ ተሻግሮ ጥቁር ሕዝቦችን ለነጻነታቸው፣ ለመብታቸው፣ ለሰብአዊነታቸውና ለክብራቸው ዘብ እንዲቆሙ አነሳስቷቸው እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ፡፡ ይህ በዓለም ሁሉ የተሰማው የቤተ ክርስቲያኒቱ በዐድዋ ዘመቻ የነበራት ውሎና ለሰው ልጆች ነጻነት ያደረገችው ተጋድሎ ለአፍሪካ፣ ለጥቁር ሕዝቦች ወኔና ትልቅ መነሳሳት ሆኗቸው እንደነበር የሚመሰክሩ ታላላቅ የዓለማችን የነጻነት ታጋዮችና የአገር መሪዎች አሉ፡፡
ይህን የታሪክ ሐቅ አስመልክቶ በአንጋፋው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እ.ኤ.አ በ2010 ዓ.ም. የክብር ዶክትሬት የተሠጣቸው የነጻነት ታጋይና የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ፕሬዝዳንት  ታቦ እምቤኪ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለአፍሪካ በተለይም ደግሞ ለደቡብ አፍሪካውያን የነፃነት ትግልና ተጋድሎ ትልቅ ኩራትና መነቃቃትን የፈጠረች መሆኗን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ልደት አዳራሽ ባደረጉት ንግግራቸው ከታሪክ በማጣቀስ እንዲህ ገልጸውት ነበር፡-
...The Ethiopian Church would the authentic African church serve as a repository of the aspirations of all Africans for freedom and respect for their cultures, their identity and their dignity. It was therefore not by accident that the independent African churches I have mentioned called themselves the Ethiopian Church ….
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እውነተኛ የአፍሪካ ቤተክርስቲያንና ለአፍሪካውያን በሙሉ ነፃነታቸው፣ ባህላቸው፣ ልዑላዊነታቸው፣ ማንነታቸውና ሰብአዊነታቸው እንዲከበር ላላቸው ህልም እንደማከማቻ ቦታ ሆና ታገለግላለች ብለው ያምኑ ነበር፡፡ ታዲያ በዚህ እውነታ እና ታሪካዊ ሐቅ ላይ ተመስርተው ነበር እነዚህ የጠቀስናቸው ቤተ ክርስቲያናት እራሳቸውን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ብለው የሰየሙት፡፡
እንግዲህ ይህ ቤተ ክርስቲያኒቱ በኢትዮጵያ፣ በአፍሪካ፣ በመላው ጥቁር ሕዝቦችና በአጠቃላይም ነጻነታቸውን በሚያፈቅሩና በሚያከብሩ የሰው ልጆች መካከል ያላት አኩሪ ታሪክ፣ ገድልና መልካም የሆነ ምስክርነት በኋላ ዘመን አፍሪካን እንደ ቅርጫ ሥጋ ለመቀራመት ለመጡ አውሮጳውያን እንደ እግር እሳት ነበር ያንገበገባቸው፡፡
እናም ይህን ለጥቁር ሕዝቦችና አፍሪካውያን መመኪያ የሆነ ታሪክ በማጠልሸት፣ ቅርሱንና ታሪኩን ከመሠረቱ በመናድ፣ በሃይማኖቱ ጽኑ የሆነውንና ለነጻነቱ ቀናዒ የሆነውን ሕዝብ ለመበቀል ሲል ፋሽስት የበቀል በትሩን በኢትዮጵያና በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ አነሳ። በቀጣይ ጽሑፌ በሰፊው የምዳስሰው የደብረ ሊባኖሱ ጭፍጨፋና እልቂትም የዚሁ በቀል ትልቅ ማሳያ ነው፡፡    
ሰላም!


Published in ህብረተሰብ

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
በጀት መዝጊያ ደረሰ አይደል! የምር ግን ከበጀቱ ጋር ሌሎች ነገሮች አብረው ቢዘጉልን አሪፍ ነበር። ልክ ነዋ…ከዓመት ዓመት ‘አልዘጋ’ ያሉ ነገሮች ኑሯችንን እያመሳቀሉብን ነው!
ስሙኝማ…እግረ መንገዴን የበጀት መዝጊያ ነገር ካነሳን አይቀር… አለ አይደል… በዓመት ለአንድ ወር ምናምን በሰኔ ‘ሲቪል ሰርቨንት’ መሆን አሪፍ ይሆን ነበር፡፡ አሀ… ዕቃው በገፍ ነዋ! አስራ ስድስት ‘ሶፍት ፔፐር’፣ አሥራ ሦስት ሳሙና፣ አሥራ ምናምን ስክሪፕቶ… ምናምን በትላልቅ ፌስታል እየሞሉ ወደቤት ነበር፡፡
ኮሚክ ነገር እኮ ነው…ልክ እኮ ‘ወገብ ፍተሻ’ በፓኬጅ የሚካሄድ ነው እኮ የሚመስለው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ… እናማ…በሦስት ወር አንዴ አንድ ጥቅል ‘ሶፍት ፔፐር’ ለመስጠት “በጀት የለም…” ምናምን ሲባል ይከርመና ሰኔ ላይ አሥራ ምናምን! እንደሱ ከሆነ አይቀር… አለ አይደል… የጤፍንም ዋጋ ቢያንስ ለክረምቱ ወራት በግማሽ መቀነስ ነዋ! አሀ…የምግብ ፍጆታ እያነሰ ‘ሶፍት ፔፐር’ ቢቆለል…ግድግዳ አንለጥፍበት! (እኔ የምለው…በሰኔ አሥራ ምናምን ‘ሶፍት ፔፐር’ አሁንም አለ እንዴ!)
እናላችሁ…ዋናው በጀት በየዓመቱ ሲዘጋ ‘መዝጊያ’ ያልተደረገላቸውና ሌላኛውን ሚሌኒየም የሚጠብቁ የሚመስሉ መአት ነገሮች አሉ፡፡
ከዓመቱ በጀት ጋር ክፋትም አብሮ ይዘጋልንማ!
የምር እኮ ዘንድሮ የሚያነጋግረው መክፋት አለመክፋታችን ሳይሆን የክፋታችን አይነትና መጠን ነው። “እከሌ ክፉ ሰው ነው…” ለማለትም እያስቸገረ ነው። ልክ ነዋ…ጠቅላላችን በየፊናችን ክፉ እያሰብንና እየሠራን ማን ማንን ሊወነጅል ይችላል!
ጓደኛ ስለጓደኛው የሚያስበው… “እንዴት ላግዘው እችላላሁ!” በማለት ሳይሆን… አለ አይደል… “እንዴት አድርጌ እገዘግዘዋለሁ…” አይነት የሆነበት የክፋት ዘመን፡፡
የአንድ እናት የአንድ አባት ልጆች… “የወላጆቻችንን ንብረት እንዴት በፍትሀዊነት እንከፋፈላለን?” ሳይሆን… “እንዴት አድርጌ ኬሎቹ በላይ ድርሻ እወስዳለሁ…” አይነት የሆነበት የክፋት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡
በሽርክና የሚሠሩ የንግድ ሰዎች… “እንዴት አብረን ከፍተኛ ደረጃ እንደርሳለን…” ከማለት ይልቅ “እንዴት እነሱን ፈንግዬ ድርጅቱን እጠቀልላለሁ…” አይነት የሆነበት የክፋት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡
እኔ የምለው… አብረን እንብላ ምናምን አለመባባል ከክፋት ነው ከብልጥነት የሚመደበው፡፡ ይቺን ስሙኝማ…ሰውየው ካፌ ቁጭ ብሎ ኬክ እየበላ ሳለ አንድ ጓደኛው ይመጣል፡፡ ሰላም ብሎት አጠገቡ ይቀመጣል። ሰውየውም “ከዚች ትንሽ ቅመስ…” የለ፣ “እዚህ ሌላ ኬክ አምጪ…” ብሎ ትእዛዝ የለ… ዝም ብሎ መብላቱን ይቀጥላል፡፡ ጓደኝየውም…
“የምትበላው ኬክ ጣፋጭ ይመስላል፣” ይለዋል።
“አዎ፣ በጣም ይጣፍጣል፡፡”
“ትልቅ ነው፣ አይደል?”
“አዎ ዳቦ ነው የሚያክለው” ብሎ ቡጢ፣ ቡጢ የሚያካክል ጉርሻውን በሹካ እየዛቀ መክተት ይቀጥላል። ጓደኛ ሆዬም…
“ታውቃለህ፣ አንተ በጎረስክ ቁጥር ከንፈሮቼ ይረጥባሉ…” ይለዋል፡፡ (ኸረ የእኛንም አንጀት ‘አንዘፈዘፍከው!’) ይሄኔ ሰውየው ምን ቢያደርግ ጥሩ ነው… “እንካ አፍህን በዚህ ጥረግ” ብሎ መሀረብ ሰጠውና አረፈ፡፡
ለጓደኞቻችሁ ኬክ መጋበዝ የማትፈልጉ መሀረብ ይዛችሁ ከቤት መውጣታችሁን አትርሱማ!
እኔ የምለው…ምን ዙሪያ ጥምጥም ያስፈልጋል! በቃ… “ከኬኩ አካፍለኝ…” ማለትን የመሰለ ቀጥታ ንግግር እያለ!
ከዓመቱ በጀት ጋር ፍረጃም አብሮ ይዘጋልንማ!
የምር ግን አንዳንድ ጊዜ ሳስበው…ዘንድሮ ‘የማይፈረጅ’ ሰው ካለ ገና ያልተፈጠረ መሆን አለበት፡፡ (ቀሺም አባባል ነው፣ አይደል!) አንድ ጊዜ ትንሽ ልጁ መዋዕለ ህጻናት ያለች ወዳጃችን ልጁ እቤት መጥታ ትምህርት ቤቷ ስለ ዘር ምናምን የሰማችውን ስትነግረው እንዴት እንዳስደነገጠው ሲነገረን ነበር። እናላችሁ… በሙያችሁ ትፈረጃላችሁ፣ በዘራችሁ ትፈረጃላችሁ፣ የእነ እከሌ ዘመድ በመሆናችሁ ትፈረጃላችሁ፣ በትዳር ጓደኛችሁ ትፈረጃላችሁ፣ በምትውሏቸውና በምታመሿቸው ሰዎች ትፈረጃላችሁ፣ በምትሰጡት ሀሳብ ትፈረጃላችሁ፣ በምታነቡት ጋዜጣና መጽሔት ትፈረጃላችሁ፣ ዝም በማለታችሁ ትፈረጃላችሁ…ብቻ ምን አለፋችሁ ዘንድሮ የማንፈራረጅበት ነገር የለም፡፡
ከዓመቱ በጀት ጋር አሉባልታም አብሮ ይዘጋልንማ!
አሉባልታ በዝቷል፡ የምር…አሉባልታ ከመብዛቱ የተነሳ እውነትና ውሸቱን ለመለየት አስቸጋሪ ሆኗል። በ‘ቦተሊካ፣’ በማህበራዊ፣ በሥራ፣ በፍቅር ግንኙነት፣ በጓደኝነት…ብቻ በሁሉም ነገር አሉባልታ በዝቷል። እናላችሁ… የብዙዎቻችን ‘ታሪክ’ እንደ ‘ታሪክ ነጋሪው’ ሆኗል፡፡
የአሉባልታ ነገር ከተነሳ አይቀር ይቺን ቀልድ ቢጤ ስሙልኝማ፡፡ ሁለት ጓደኛሞች እያወሩ ነው፡፡
“እሷ ልጅ ቦይ ፍሬንድ የማይቆይላት ለምንድነው?”
“መቼም ታውቃለህ ቦይ ፍሬንድ ገርል ፍሬንድ ‘ኪሶሎጂ’ ምናምን አለ፡፡”
“አዎ፣ ግን ይሄ ከእሷ ጋር ምን ግንኙነት አለው?”
“ቀኑን ሙሉ ያለማቋረጥ ስለምትለፈልፍ ቦይፍሬንዶቻቸው ምን ሰዓት ይሳሟት!”
አትታያችሁም! እንዲህ ከመባልስ ለምን አንድ ዓመት ሙሉ ዝም ጭጭ አይባልም! እንትናዬዎች ወሬያችሁን ቀንሱማ፡፡
የወሬ ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…ሁለቱ ጓደኛሞች ሲያወሩ አንደኛው…
“ጓደኛዬ ሚስቱን ለሦስት ዓመት አንድም ነገር ብሏት አያውቅም፣” ይላል፡፡ ያኛውም…
“ለምን?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው…
“እሷ አውርታ ስላልጨረሰች ተራውን እየጠበቀ ነዋ!”
እኔ የምለው ሀሳብ አለን….እንትናና እንትናዬዎቹም ይሄ የአሮጌ በጀት መዝጋትና አዲስ በጀት መንደፍንም ቢያስቡበት አሪፍ ነው፡፡ ልክ ነዋ… አሀ ሁልጊዜ ‘ጉልበት’ የለ….! ይኸው ዌይን ሩኒ እንኳን ጉልበት እያነሰው አይደል! ቂ…ቂ…ቂ…
ስለዚህ እንትናና እንትናዬዎች የአዲሱን ዘመን በጀት ስታወጡ እንደ መነሻ ሀሳብ ሊሆን የሚችል ጥቆማ… “እነሆ በረከትን በተመለከተ አዲስ የበጀት ቀመር ማውጣት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። በመሆኑም በአቅም መዳከም የተነሳና ጉልበት ለመመለስ የጤፍና የቅቤ ዋጋ ይወርዳል ተብሎ ስለማይታሰብ… እነሆ በረከት በወር አንድ ጊዜ ብቻ ይሆናል፡፡ አስፈላጊ ሆኖ በተገኘ ጊዜም በሦስት ወር አንዴ ሊሆን ይችላል…” ምናምን ማለት ይቻላል፡፡
ከዓመቱ በጀት ጋር በ‘አገር ልጅ መቧደን’ አብሮ ይዘጋልንማ!
“የወንዜ ልጅ…” “የአገራችን ልጅ…” እየተባለ ‘የቡድንና የቡድን’ አባቶች በዝቷል፡፡
“እሱ መሥሪያ ቤትማ እንትኖች ብቻ ናቸው የተሰበሰቡበት…”
“ጠቅላላ እኮ የቅርብና የሩቅ የሥጋ ዘመድ ነው ድርጅቱን የያዘው…”
“ሥራ አስኪያጁ እኮ በችሎታ ሳይሆን የአገር ልጅነት እያየ ነው የሚቀጥረው…”
አይነት አስተያየቶችን መስጠት የለመደብን ወደን አይደለም፡፡ በርካታ ሰዎችን የሚያስተዳድሩ ድርጅቶች እንኳን ክፍት ቦታዎች የሚሞሉት በ‘ወንዜ ልጅነት’ ሲሆን አሪፍ ‘ስልጣኔ’ አይደለም፡፡
የምር እኮ… በምግብ ቤቶች እንኳን በ‘አገራቸው አፍ’ ሲያናግሯቸው ባዶው ሜዳ እንኳ ‘እስኪያደናቅፋቸው’ የሚሯሯጡ አስተናጋጆች ይገጥማሉ፡፡ “እንትናዬ…ሥራ አስኪያጁ የአገራችን ሰው ነው አሉ፡፡ ለምን ሄደሽ አታናግሪውም!” ተብለሽ አታውቂም!
እናላችሁ… ከዓመቱ በጀት ጋር አብረው ቢዘጉልን የምንመኛቸው መአት ነገሮች አሉ፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Published in ባህል

በቱርክ ባለሀብቶች በሚመሩት ፋብሪካዎች የተቀጠሩ ሠራተኞች የመብት ረገጣ ይደርስብናል አሉ  

በመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት አስተባባሪነት ሰሞኑን ለሶስት ቀናት የዘለቀ፣ ከአዲስ አበባ ተነስቶ አዳማን ያካለለ የፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪ ተቋማት ጉብኝት ተካሂዶ ነበር። ጉብኝቱን የጀመርነው  ከአንድ ወር በፊት ተመርቆ በምርት ሂደት ላይ የሚገኘውን በብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን የኢትዮጵያ ፓወር ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ (ሜቴክ) በሚል ስያሜ ከሚታወቀው መንግስታዊ የኤሌክትሪክ ትራንስፎርመር ማምረቻ ፋብሪካ ነው፡፡
የኮርፖሬሽኑ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ አማኑኤል አብርሃ ለጋዜጠኞች እንደገለፁት፤ ፋብሪካው በአገሪቱ እየተከናወኑ ላሉት ታላላቅ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግንባታዎች አስፈላጊ የሆኑ ትራንስፎርመሮችን በማምረት ያቀርባል፡፡ ቀደም ሲል በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ይመጡ የነበሩ ትራንስፎርመሮችን ከማስቀረቱም በላይ በቀጣይ ምርቶቹን ወደተለያዩ አገራት ለመላክ የሚያስችል ዕቅድ ተይዟል፡፡ ለፋብሪካ ማስፋፊያ ሥራው ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን የገለፁት ሻለቃ አማኑኤል፤ ፋብሪካው የውጭ ምንዛሪን በማዳን፣ በአገር ውስጥ ቴክኖሎጂ በጥራት ላይ በማተኮር እንደሚንቀሳቀስም ገልፀዋል፡፡
ቀጣዩ የጋዜጠኞች ጉብኝት በቢሾፍቱ ከተማ ውስጥ የሚገኘውና በህንድ ባለሃብቶች የሚተዳደረው “ካኖሪያ አፍሪካ” የተባለው የጅንስ ማምረቻ ፋብሪካ ነበር። የፋብሪካው ግንባታ ተጠናቆ ወደ ምርት ሂደት ከገባ ጥቂት ጊዜያት ያስቆጠረ ሲሆን ፋብሪካው ከ500 በላይ ለሚሆኑ ሠራተኞች የሥራ ዕድል የከፈተና አምስት ሺህ ለሚሆኑ የጥጥ አምራች ገበሬዎች የገበያ ዕድል ያመቻቸ መሆኑ በጉብኝቱ ላይ ተገልፆልናል፡፡ በምሥራቅ አፍሪካ የመጀመሪያው ነው በተባለው በዚህ ፋብሪካ ውስጥ የአሜሪካ፣ የጀርመንና የጃፓን ስሪት የሆኑ፣ እጅግ ዘመናዊ ማሽኖች እንደተተከሉም ተነግሮናል፡፡ ፋብሪካው በ40 ሚሊዮን ዶላር ካፒታል የተቋቋመ ነው ተብሏል፡፡  
 በፋብሪካ ውስጥ በጉልበት ሥራ ላይ ተሰማርተው ከሚሰሩ ሠራተኞች መካከል አንዳንዶቹን ባነጋገርንበት ወቅት እንደገለፁልን፤ በሥራው ላይ ለጤና ሥጋት ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮችን ለማስቀረት የሚያስችልና ለሠራተኛው ደህንነት የሚጠቅም አንዳችም ነገር የለም፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ሠራተኞቹ ከብናኝና ሌሎች ለጤና ጐጂ ከሆኑ ነገሮች ጋር በቅርበት የሚሰሩ ቢሆንም እነዚህን ችግሮች ለመከላከል የሚያስችል ምንም አይነት መከላከያ እንደሌለ ይናገራሉ፡፡ ሠራተኞቹ በህብረት የመነጋገር፣ ለመብታቸው የመከራከርና ጥቅማቸውን የማስጠበቅ ዕድል እንደተነፈጉም ገልፀውልናል፡፡ የሠራተኞች መቀያየር የተለመደ መሆኑን የሚናገሩት ሠራተኞቹ፤ ከሥራው ለጤና ጎጂ መሆን አንጻር ረዘም ላለ ጊዜ በሥራ ላይ የሚቆይ ሠራተኛ እንደሌለ ነው የነገሩን፡፡  
በቅርቡ የተመረቀው የአዳማው የንፋስ ኃይል ማመንጫ በጋዜጠኞች ከተጐበኙት የልማት ሥራዎች አንዱ ነበር፡፡ ይህ ጉብኝት ሲጠናቀቅም በመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት አስተባባሪነት የሚመራው  የጋዜጠኞች ቡድን፣ ቀጣይ ጉብኝቱን ለማድረግ ጉዞውን ያቀናው በቱርክ ባለሃብቶች ወደሚመራው ELSE Addis የተባለ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ነበር፡፡ በዓመት 500 ቶን የክር ምርቶች ምርቶችን እያመረተ ወደ ኢጣሊያ፣ ቱርክና ስፔን የሚልከው ይህ ፋብሪካ፤ ከፍተኛ የማምረት አቅም ያለው ግዙፍ ፋብሪካ ነው፡፡
ቱርካውያኑ የፋብሪካው የሥራ ኃላፊዎች ለጉብኝት የሄደውን ጋዜጠኛ ተቀብለው ፋብሪካውን በቅጡ ለማስጐብኘትና ስለሚያመርቷቸው የክር ምርቶች ጥንካሬና ተፈላጊነት ለመግለጽ የተጉትን ያህል ጋዜጠኞች የፋብሪካውን የጉልበት ሠራተኞች አግኝተው ለማናገር እንዳይችሉ በእጅጉ ተከላክለዋል፡፡ አንድ ፊቱን በሥራ ላይ ወደነበሩ ሠራተኞች አዙሮ የነበረ ጋዜጠኛ፤ የፋብሪካው የጸጥታ ኃይሎች በሚመስሉ ሰዎች ሠራተኞችን ማነጋገር እንደማይችልና በጉብኝቱ ላይ ብቻ ማተኮር እንደሚገባው ተነግሮታል፡፡ በተለይ አንዲት ኢትዮጵያዊት (የፋብሪካው የደህንነት ሠራተኛ ትመስላለች) ይህን መሰሉን ተግባር በትጋት ስትከውነው ተስተውላለች፡፡ ከእነሱ እይታ ተከልለን ሠራተኞቹን ለማናገር የሞከርን ጋዜጠኞች  በቪዲዮ ካሜራ በታገዘው የቱርካውያኑን ክትትል ሥር መሆናችንን የተረዳነው፣ “ሠራተኞቻችንን አታናግሩብን” የሚል ቁጣ ዳግም ሲመጣብን ነበር፡፡ ይሄኔ ነበር የፋብሪካውን ሥራ አስኪያጅ አስጠርተን፣ ሠራተኞቹን ማናገር እንደምንፈልግ በመግለጽ ፍቃድ እንዲሰጠን የጠየቅነው፡፡
ሥራ አስኪያጁ ሠራተኞቹን ማናገር መብታችን እንደሆነ ገልፀው፣ የፈለጋችሁትን አነጋግሩ ቢሉንም የጸጥታ ሠራተኞቹን በካሜራ የታገዘ ክትትልን ግን ሊያስቀሩልን አልቻሉም፡፡
ሁኔታው ያስፈራቸው ኢትዮጵያውያን የጉልበት ሠራተኞችም በዚያ ሁኔታ ውስጥ ሃሳባቸውን መግለጽ እንደማይችሉ ጠቁመዋል፣ ለቃለመጠይቁ ፈቃደኛ ሳይሆኑልን ቀሩ፡፡ በተለያዩ መንገዶች ከሥራ ውጪ አግኝተን ያነጋገርናቸው የፋብሪካው ሠራተኞች፤ በፋብሪካው ውስጥ በሚሰሩ የጉልበት ሠራተኞች ላይ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ረገጣ እንደሚደርስባቸው፣ ሃሳባቸውን በነፃነት የመግለጽ መብት እንደሌላቸው፣ ለጤናና ለህይወት በጣም አደገኛ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እየሠሩ እንደሚገኙና የሚከፈላቸው ደመወዝ እጅግ አነስተኛ (በወር 900 ብር) እንደሆነ ገልፀውልናል። በወቅቱ በጋዜጠኞች በቦታው መገኘት የተነሳ፣ በቱርካውያኑ “የክልከላ ሠራተኞች” ላይ ያየነው መደናገጥና ከሠራተኞቹ ጋር እንዳንገናኝ ለማከላከል ሲደረግ የነበረው ጥረት   እንደሚባለውም በሠራተኞች አያያዝ ላይ ችግር እንዳለ ጠቋሚ ነው፡፡
የዚህ ፋብሪካ ሰራተኛ የሆነ አንድ ወጣት በሰነዘረው አስተያየት፤ “መንግስታችን ርካሽ የሰው ጉልበት አለን ብሎ የውጪ ኢንቨስተሮችን ሲያመጣ፣ ርካሽ የሰው ህይወት አለን ያላቸው መስሏቸው ነው” ሲል  በሠራተኞቹ ላይ የሚደርሰውን በደል በስላቅ ገልጿል፡፡
በጉብኝቱ ላይ አብረውን ለነበሩ የአሰሪዎችና ሰራተኞች ጉዳይ የሚመለከታቸው የመንግስት ሃላፊ በሰራተኞቹ ላይ ይደርሳል ስለተባለው በደል አንስተንባቸው በሰጡት ምላሽ፤ “ሠራተኞች በህብረት ተደራጅተው ማህበር በማቋቋም ለመብታቸው መታገል እንደሚችሉ” ገልፀውልናል፡፡ በቱርኩ ፋብሪካ ውስጥ የሚሰሩ ሠራተኞች ግን እንኳንስ የመደራጀት ሁለት ሦስት ሆነው ለማውራትም እንደማይፈቀድላቸው ነው የተናገሩት።
የውጭ ኢንቨስተሮች የአገሪቱን ኢኮኖሚ በማሳደግ፣ ሰፊ የስራ ዕድል በመክፈት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ ወዘተ የማይናቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ የታወቀ ነው፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያውያን ሠራተኞች መብት ቢያንስ በገዛ አገራቸው ሊከበርላቸው ይገባል፡፡ በውጭ ኢንቨስተሮች ለኢትዮጰያውያን የሚከፈለው ደሞዝም ዝቅተኛ ጣራ በህግ የተደነገገ መሆን ይኖርበታል፡፡ መቼም መንግስት ርካሽ የሰው ጉልበት አለኝ ሲል የሚበዘበዝ የሰው ጉልበት አለኝ እያለ እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ ይሄንን ግን በውሎችና በህጎች ሊያስረውና ለዜጎቹ መብት ሊቆም ይገባል፡፡       


ከዕለታት አንድ ቀን የዱር አራዊት ንጉሥ “አያ አምበሶ ታሟል እና ሄደን እንጠይቀው” ብለው የዱር አራዊት እመት ጦጢትን ይነግሯታል፡፡
እመት ጦጢትም፤
“እስቲ እናንተ ቀደም ብላችሁ ሂዱ፡፡ እኔ፤ አያ አምበሶ የሚመገበውን ምግብ ለማዘጋጀት የሚጠቅመውን ራሺን ልሸማምት” አለቻቸው፡፡
የዱር አራዊቱ ወደ አያ አምበሶ ሄዱ፡፡ ጦጢት ወደ ኋላ ቀርታ ዝም ብላ የሚሆነውን ታዳምጥ ጀመር፡፡
የዱር አራዊቱ አያ አምበሶ ጋ ደርሰው፣
“አያ አምበሶ ተሻለዎ ወይ?” ይላሉ፡፡
አያ አምበሶም፤
“ኧረ እየባሰብኝ ነው የመጣው፡፡ እርጅናም በጣም እየተጫነኝ ነው፡፡ በዛ ላይ የሚያስታምመኝ አንድም እንስሳ አጠገቤ የለም፡፡ ደግም ምግብ እንደልቤ አልበላም” አለ፡፡
ሁሉም ደንግጠው “ምን ብናደርግ ይሻላል?” ተባባሉና “ምን ዓይነት ምግብ ያምርዎታል?” ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡
አያ አምበሶ፤ “በየቀኑ የሚያምረኝ ሥጋ ዓይነቱ ይለያያል
አንድ ቀን የድኩላ ያምረኛል፡፡
ሌላ ቀን የጎሽ ያምረኛል፡፡
ደሞ ሌላ ቀን የቀጭኔ ሥጋ እንደጉድ ያምረኛል፡፡  
ደሞ አንዳንድ ሰሞን የነብር ሥጋ ያስፈልገኛል፡፡ ይሄን ካላገኘሁ የምድን አልመሰለኝም” አለ፡፡ የዱር አራዊቱ ደግመው ተሰበሰቡና፤
“ጎበዝ ምን እናድርግ?” ተባባሉ፡፡
ሁሉም፤ “ጦጣ መላ አታጣም፡፡ ሄደን እንጠይቃት” አሉ፡፡
ከአያ አምበሶ ጊዜ ቀጠሮ ወሰዱ፡፡ ሀሳባቸውን በደምብ አብስለው እስኪመጡ ተራ ገብተው ሊያስታምሙ ተስማሙ፡፡
ጦጢት እንዳደፈጠች ዛፉዋ ላይ ሆና ትጠብቃለች፡፡ ወደ እሷው ዘንድ ሄዱና፤
“እመት ጦጢት አያ አምበሶ ግራ - የሚያጋባ ጥያቄ አቀረቡልን፡፡ ይኸውም ከየአንዳንዱ እንስሳ በዓይነት በዓይነቱ ምግብ ያምረኛል አሉ፡፡ ይህን እናድርግ ካልን በቀን በቀን አንድ አንድ እንስሳ ይታረድ እንደማለት ነው?” አሏት
እመት ጦጢትም፤
“ይሄ መቼም ዐይናችን እያየ እያንዳንዳችን በየተራ እንሙት ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የሚሻለው አንድ ሆነን፣ በአንድ ድምፅ፣ ፈትልና ቀስም ሆነን፤ ይሄ የማይሆን ምኞት ነው፡፡ የታመመ፣ ወይም ጊዜው የደረሰ እንስሳ ካገኘን እናቀርብልዎታለን፡፡ አለበለዚያ ግን ምንም የምንረዳዎት ነገር የለም፤ እንበል፡፡ ግን አንድ ልብ ይኑረን!” አለች፡፡ የዱር አራዊቱ በጦጣ ሀሳብ ተስማሙ፡፡
እንደተባባሉት ዋና ተናጋሪ መርጠው ለአያ አምበሶ የወሰኑትን ውሳኔ ገለጡ፡፡
አያ አምበሶ፤ በየቀኑ ምን ምን የምግብ ዓይነት መርጠው ይሰጡኝ ይሆን? እያለ በጉጉት ሲጠብቅ የወሰኑትን ሲሰማ፤ ባለበት በድን ሆኖ ቀረ፡፡ በዚያው ህይወቱ አለፈ፡፡
*    *     *
አለቃ ምንዝሩን የሚያጠቃበት፣ ሥርዓቱን ለግል ጥቅሙ ለማዋል የሚሯሯጥበት፣ አልፎ ተርፎም የደጋፊዎቹን ህልውና ሳይቀር የሚያናጋበት ሁኔታ ከፈጠረ ጤና አይኖርም፡፡ ሥርወ - መንግሥቱም የረጋ አይሆንም፡፡ ዛሬ በሚሊዮንና በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ፕሮጀክት፣ ህንፃ፣ ፋብሪካ ወዘተ የሚወራበት አገር ነው ያለን፡፡ የህዝቡ ኑሮ ግን ፈቀቅ አላለም፡፡ ምናልባት የህንድ ዓይነት ጥቂቶች ከዝሆን ጥርስ የተሰራ ፎቅ ማማ ላይ ያሉ የናጠጡ ሀብታሞች ከአናት የተቀመጡባት፣ በአንፃሩ ህልቆ መሳፍርት ድሆች የጉስቁልና ህይወት የሚመሩባት አገር እንዳትሆን መስጋታችን አልቀረም፡፡ ማባሪያ የሌለው ምዝበራና ሙስና ጓዳ - ደጁን ሞልቶት፣ በህጋዊ መንገድ ያልተገኘ ብልፅግና ሥር የሰደደበት ሁኔታ እያለ ዕድገት ማምጣት ከባድ ነው፡፡ ሀንቲግተን ዘመናዊነትና ሙስና በሚለው ሀተታው፤ “ሙስና የባለሥልጣናት ጠባይ ሲሆን፤ ከተለመደው ህግ በማፈንገጥ ሥልጣንን ለግል ጥቅም ማዋል ነው … በእርግጥም ሙስና ስኬታማ ፖለቲካዊ ተቋም አለመኖር ምልክት ነው!” ብሏል፡፡
የሲቪል ተቋማት አለመኖር (Civic Society) የዲሞክራሲ መዳከም ምልክት መሆኑን የፖለቲካ ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡ ይህን መሰል ተቋማት ብዙ ያስፈልገናል። ለውጥ በመጣ ቁጥር አዳዲስ ሹማምንትን ማየት የተለመደ ነው፡፡ የምናያቸው ሹማምንት ፊት ካየናቸው የተሻሉ እንዲሆኑ እንመኛለን/እንናፍቃለን፡፡ ያንን ካላገኘን “ሣር የምትበላው በቅሎ ሄዳ ልጓም የምትበላው መጣች” የሚለው ተረት ዕውን እንዳይሆን ያሰጋል!! ከዚህ ይሰውረን!

Published in ርዕሰ አንቀፅ
Saturday, 20 June 2015 10:13

‹‹እውነት!?››

‹‹እውነት!?››
አንድ የገዢው ፓርቲ አባል ‹‹ምርጫ በማሸነፉ›› ደስ ተሰኝቶ ሚስቱ ጋ ደወለ አሉ፡፡
‹‹ሄሎ ማሬ!›› ‹አቤት ውዴ! ‹‹ምርጫውን እኮ አሸነፍኩኝ!›› አለ ደስታ ባመጣው ፈገግታ ታጅቦ፡፡ ‹‹እውነት!?›› እሷም ደስታ የሚያደርጋትን አሳጥቷት ባለማመን ጠየቀች፡፡ ጥያቄዋ ግን ባልን አስቆጣው፤ ‹‹እ!? ምን አልሽ አንቺ!›› ‹‹እውነት አሸነፍክልኝ ወይ?› ነው ያልኩት፡፡›› አሁንም ደስታዋ አላባራም፡፡
‹‹አንቺ ሴት ከፀረ ሰላም ኃይሎች ጋር መዋል ጀመርሽ ማለት ነው!?›› ንዴት የሚያደርገውን እያሳጣው፡፡
‹‹ምን እያልክ ነው ውዴ?›› ግራ ቢገባት ጠየቀች፡፡
‹‹እዚህ ጋ ‹እውነት› የሚለውን ቃል ምን አመጣው!? ‹አሸነፍኩ› ማለት፤ ያው አሸነፍኩ ነው! አይገባሽም እንዴ!››
(ከበኃይሉ ገ/እግዚአብሄር ፌስቡክ)

Published in ህብረተሰብ

     ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በወጣው የአዲስ አድማስ ዕትም ላይ በብዙዎች የተዘነጋውንና ከህወሓት 10 መስራቾች አንዱ የነበረውን የታጋይ አብጠው ታከለን ታሪክ ጋዜጣችሁ ለህዝብ ለማስተዋወቅ ያደረገውን ጥረት እናደንቃለን፤ምስጋናችንንም  እናቀርባለን፡፡ምንም እንኳን የአባታችን የትግል ታሪክ ተገቢውን ዕውቅና እንዲያገኝ ለሚመለከታቸው የፓርቲና የመንግስት ባለሥልጣናት ለማስታወስ  ከጎንደር አዲስ አበባ በመጣን ጊዜ የሚያነጋግረን አጥተን ብንከፋም፣ ጉዳያችንን ለማስረዳት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ (ነፍሳቸውን ይማርና) ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን ቢሮ በሄድንበት ወቅት በታላቅ ክብር፣ ከመቀመጫቸው
ተነስተው በመቀበል  ስላስተናገዱን ልናመሰግናቸው እንወዳለን፡፡ ይሄም ብቻ አይደለም።  ወይዘሮ
አዜብ “ጉዳያችሁ ጉዳዬ ነው” ብለው ታጋይ አብጠውን በተመለከተ የሚቻለው ሁሉ እንዲደረግ የበኩሌን ያለሰለሰ ጥረት አደርጋለሁ በማለት በእጅጉ አበረታተውናልና በድጋሚ ከልብ እናመሰግናለን፡፡ አባታችን አቶ አብጠው ታከለ፤ ከህውሓት የትግል ጥንስስ ጀምሮ ህይወቱ እስካለፈችበት 2000 ዓ.ም ድረስ ከኢህአዴግ የትግል መስመር ያልወጣና በያዘው አቋም የፀና እንደነበርም በዚህ አጋጣሚ እንዲታወቅልን እንፈልጋለን፡፡
ቤተሰቦቻቸው 

ትርፉ ከ30 ሚ. ወደ 1.5 ሚ አሽቆልቁሏል ተብሏል
ካፒታሉን በአስተማማኝ ደረጃ እያሳደገ ነው - አመራሩ

    አልፋ የትምህርትና ስልጠና አክሲዮን ማህበር በአስተዳደር ድክመት ለኪሳራና ለውድቀት እየተዳረገ ነው ሲሉ አንዳንድ ባለአክሲዮኖች ስጋታቸውን የገለፁ ሲሆን የማህበሩ ስራ አመራር ቦርድ በበኩሉ፤ አክሲዮኑ ቋሚ ንብረት እየፈራ በመሆኑ የኪሣራና የውድቀት ስጋት የለበትም ብሏል፡፡ ኩባንያው ባለፉት 7 አመታት አመታዊ ትርፉ፣ የተማሪዎች ቁጥርና ተደራሽነቱ እያሽቆለቆለ መምጣቱን የሚገልፁት ቅሬታ አቅራቢዎች፤ ኩባንያውን ከገባበት ቀውስ ለማውጣት አሁን ያለው ቦርድም ሆነ ስራ አመራር ጥረት ሲያደርግ አይታይም ብለዋል፡፡ አሁን ያሉት የስራ አመራሮችም ሆኑ የቦርድ አባላት በሌላ መተካት እንደሚገባቸው በተደጋጋሚ ማመልከታቸውን የሚጠቅሱት ከቅሬታ አቅራቢዎቹ አንዱ አቶ ሽፈራው ተስፋዬ፤ አሁን ያለው የስራ አመራርም ሆነ የቦርድ አባላት በአክሲዮኑ ላይ ለደረሰው ኪሣራና ውድቀት ተጠያቂ ናቸው ይላሉ፡፡
አመራሩ በኩባንያው ላይ አድርሷል ያሉትን ጉዳትም ይጠቅሳሉ - አቶ ሽፈራው፡፡ ባለሀብቱን በማሳተፍና የቢዝነስ አማካሪዎችን በማስጠናት የኩባንያው ችግሮች ታውቀው መፍትሔ እንዲፈለግ ባለማድረጉ፣ የተማሪ ቁጥር እንዳይቀንስ ከተቻለም እንዲጨምር ምንም ዓይነት ጥረት አለማድረጉን ቅሬታ አቅራቢው ገልፀዋል፡፡
ኩባንያው በፊት ከነበረው በአመት 30 ሚሊዮን ትርፍ ወደ 1.5 ሚሊዮን ብር አመታዊ ትርፍ መውረዱን የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ አዳዲስ ተማሪዎችን ወደ አልፋ ለመሳብ ምንም አይነት ጥረት ባለመደረጉ በ2000 ዓ.ም ከነበረው የርቀት ተማሪ ቁጥር ከ20ሺህ በላይ ቀንሷል ይላሉ፡፡ ብዙ ሺህ ተማሪ መያዝ በሚችል ህንፃ በአሁን ወቅት 141 ተማሪዎች ብቻ በመደበኛ የድግሪ ፕሮግራም እየተማረ ነው የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ የኩባንያው የሠራተኛ ቁጥርም እየቀነሰ ነው፤ እስከ 100 የሚደርሱ ሠራተኞች የተባረሩበት ሁኔታም አለ ብለዋል፡፡ አንዳንድ የትምህርት መስኮችም እስከመዘጋት መድረሳቸውን የሚጠቅሱት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ይህ ሁሉ ሲሆን አመራሩ ምንም አይነት የማስተካከያ እርምጃ አለመውሰዱን ጠቁመው አመታዊ የአክሲዮን ክፍፍል ድርሻችንም እጅግ አሽቆልቁሏል ይላሉ፡፡ የኩባንያው የስራ አመራር ሰብሳቢ ዶ/ር ብርሃኔ አስፋው ከባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ለቅሬታዎቹ በሰጡት ምላሽ፤ አክሲዮን ማህበሩ 1960 ባለአክሲዮኖች
እንዳሉት ጠቁመው፣ “ኩባንያው ለረጅም ጊዜ ትርፋማ ሆኖ ዘልቋል፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የተለያዩ የግል ህንፃዎችንና ት/ቤቶችን በመገንባት ቋሚ ንብረቶቹን አስተማማኝ አድርጐ ካፒታሉን ወደ 125 ሚሊዮን ብር አሳድጓል” ብለዋል፡፡ አልፋ የተቋቋመው በዋናነት ትምህርትን ለማስፋፋት ነው ያሉት ዶ/ር ብርሃኔ፤ በዚያው ልክ ባለድርሻዎቹን ተጠቃሚ ለማድረግ በየጊዜው አዳዲስ ፕሮጀክቶችን እየቀረፀ ካፒታሉን በማሳደግ
ላይ መሆኑን ተናግረዋል። የተማሪዎች ቁጥር አሽቆልቁሏል፣ ትርፉም ቀንሷል የሚለውን ቅሬታ በተመለከተም በየአመቱ የተማሪ ቁጥር ሊያሽቆለቁል የቻለው በፊት ብቸኛው የርቀት ትምህርት ሰጪ ስለነበር ነው ያሉት ዶ/ር ብርሃኔ፤ አሁን የግልና የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች በአማራጭነት በገበያው በመቀላቀላቸው የተፈጠረ የገበያ ድርሻ ማጣት መሆኑን ተናግረዋል - ዶ/ር ብርሃኔ፡፡ አልፋ እነዚህ አዳዲስ የገበያ ተጋሪዎቹ በመምጣታቸውም ደስተኛ ነው፤ ገበያዬን ተሻሙኝ የሚል ቅሬታ የለውም ያሉት ዶ/ር ብርሃኔ፤ “እኛ ባለአክሲዮኖች አስተማማኝ ሃብት እንዲኖራቸው በየቦታው ህንፃዎችን በመገንባት፣ ከመማር ማስተማር ጐን ለጐን ቋሚ ንብረት እያፈራን ነው” ብለዋል፡፡ የተማሪ ቁጥር አነስተኛ ለመሆኑ ሌላው ምክንያት ብለው ሃላፊው ያቀረቡት “ኩባንያው ከብዛት ይልቅ ለጥራት ቅድሚያ መስጠቱ ነው፤ አላማውም ጥራት ያለው የሠለጠነ የሰው ሃይል በማፍራት በስራው ዓለም ተመራጭ የሆኑ ተማሪዎችን ማፍራት ነው” ይላሉ፡፡ “የተማሪ ቁጥር በመቀነሱ ትርፋችን ቀንሷል ብለን አልተደናገጥንም” ያሉት ዶ/ር ብርሃኔ፤ ብዙ ቋሚ ሃብት መፍጠራችን ሌላው ስኬታችን ነው ብለዋል፡፡ የአንዳንድ ባለአክሲዮኖች ቅሬታ የመነጨውም በፊት ሲገኝ የነበረው ትርፍ አሁን በመቀነሱ ነው ያሉት የቦርዱ ሊቀመንበር፤ ኩባንያው ግን አዳዲስ ፕሮጀክቶችን እየቀረፀ በየጊዜው ካፒታሉን በአስተማማኝ ደረጃ እያሳደገ ነው ብለዋል። ትርፉም ቢሆን በአስጊ ደረጃ እየቀነሰ አለመሆኑን ያስረዱት ዶ/ር ብርሃኔ፤ አሁንም ኩባንያው አትራፊ መሆኑንና ከስሮ እንደማያውቅ ተናግረዋል፡፡ “የትምህርት ዘርፍ እንደሌላው ንግድ አይደለም፤ ብዙዎቻችን በዚህ ዘርፍ የተሠማራነው ጥራት ያለው ትምህርት ከሠጠን፣ ለወደፊት አትራፊ መሆን እንደምንችል በማሰብ ነው” ብለዋል - ዶ/ር ብርሃኔ፡፡   

Published in ዜና

በኦሮሚያ 2 አባላት ተገድለዋል፤ 640 ታስረዋል ብሏል

መድረክ በደቡብ ክልል ሃዲያ ዞንና በትግራይ ክልል ሁለት አባላቱ በ3 ቀናት ልዩነት እንደተገደሉበት አስታወቀ፡፡ ባለፈው ማክሰኞ በትግራይ ክልል የመድረክ አባል የነበረው አቶ ታደሰ አብርሃ እንደተገደለበት
በመግለጫው ያስታወቀ ሲሆን ከትናንት በስቲያ ሐሙስ ደግሞ በደቡብ ክልል ሃዲያ ዞን አቶ ብርሃኒ ኤረቦ የተባሉ የመድረኩ አባል ተገድለው ትናንት ጠዋት አስከሬናቸው መገኘቱን የመድረክ ሊቀመንበር ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ በምዕራብ ትግራይ ዞን የአረና/መድረክ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ሆነው በዘንድሮው ምርጫ በዞኑ የምርጫውን ሥራ በማደራጀት፣ በመቀስቀስና ታዛቢዎችን በመመደብ ከፍተኛ ሚና ሲጫወቱ የቆዩት አቶ ታደሰ አብርሃ አርአያ በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ተደብድበው መገደላቸውን መድረክ
አስታውቋል፡፡ ባለፈው ማክሰኞ ከምሽቱ 3 ሰዓት ላይ ለጊዜው ማንነታቸው በግልጽ ተለይቶ ያልታወቁ 3 ሰዎች  ወደ ቤታቸው በመግባት በተፈጸመባቸው አሰቃቂ ድብደባ ሕይወታቸውን ያጡት አቶ ታደሰ፤
በምርጫው ቅስቀሳ ወቅትም በኢህአዴግ ካድሬዎችና ታጣቂዎች ድብደባ ተፈጽሞባቸዋል ያለው
መድረክ፤ “ምርጫውሲያልፍ አንድ በአንድ እንለቅማችኋለን፤ የትም አታመልጡንም” የሚል ዛቻና ማስፈራሪያም ደርሶባቸው ነበር ብሏል፡፡
በዞኑ በሚገኘው ማይካድራ ከተማ ነዋሪ የነበሩት አቶ ታደሰ አብርሃ፤ ድብደባው እንደተፈጸመባቸው ጉዳዩን የሰሙት አቶ መሰለ ገ/ሚካኤል /በዞኑ የአረና/መድረክ ተወካይ/ ለጉዳተኛው የሕክምና ዕርዳታ እንዲደረግላቸው ለማስተባበርና ወንጀለኞችንም ተከታትሎ ለማስያዝ  ከቤታቸው በሞተር ብስክሌት ወጥተው ሲንቀሳቀሱ ፖሊሶች ይዘው “መንጃ ፈቃድ በእጅህ አልያዝክም” በሚል ሰበብ ሞተር ብስክሌታቸውን ወስደው ፖሊስ ጣቢያ በማስገባታቸው፣ለተጎጂው ከመድረሳቸው በፊት ሕይወታቸው ማለፉን  መድረክ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡ የ48 ዓመቱ ጎልማሳ አቶ ታደሰ አብርሃ፤ ባለትዳርና የአንድ  ሴት ልጅ አባት የነበሩ ሲሆን የቀብር ሥነ ሥርዓታቸውም በነጋታው ረቡዕ ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች በተገኙበት  ተፈጽሟል ብሏል፡፡በሌላ በኩል በትግራይ ክልል በምርጫው ሰሞን ዕጩዎች በሚቀርቡበት ወቅት የታሰሩ 17

የአረና/መድረክ አባላት አሁንም በመቀሌ ወሕኒ ቤት ታስረው እንደሚገኙ መድረክ አስታውቋል፡፡ በደቡብ ክልል የተለያዩ ዞኖች እና ወረዳዎችም በአባላቱና በምርጫው ወቅት በታዛቢነት ያገለገሉ ግለሰቦች ላይ የተለያዩ መከራዎችና እንግልቶች እየተፈፀሙ መሆኑን የፓርቲው መግለጫ ጠቁሟል፡፡ በእሳት ቤት ንብረትን ማቀጠልን ጨምሮ ከቤት ማፈናቀልና እስራት በአባላትና ደጋፊዎች ላይ እየተፈፀመ ነው ያለው መድረኩ፤ “ተቃዋሚዎችን መርጣችኋል ወይም ህዝቡ እንዲመርጣቸው ቀስቅሳችኋል” በሚል ግለሰቦችን ማሰቃየቱና ማዋከቡ ተጠናክሮ እንደቀጠለ አስታውቋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎችም ከምርጫው ዋዜማ ጀምሮ እስካሁን
640 አባላትና ደጋፊዎቹ መታሰራቸውን የጠቀሰው መድረኩ ሁለት አባላት ሲገደሉ 66 መደብደባቸውን፣ 7 አባላቱም በጥይት ተመተው እንደቆሰሉ መድረክ በመግለጫው አመልክቷል፡፡ በመድረኩ አባላት ላይ እየደረሰ ያለውን ግድያ፣ እንግልትና ስቃይ በተመለከተ በዝርዝር ለምርጫ ቦርድ አቤቱታ ማቅረባቸውን የጠቆሙት የፓርቲው ሊቀመንበር ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ “በአባላቶቻችን ላይ እየደረሰ ባለው ግድያ የአህያ ባል ከጅብ አያስጥልም እየሆነብን ችግር ላይ ነው ያለነው” ብለዋል፡፡ መንግስት በጉዳዩ ላይ ሊያነጋግራቸው እንደሚገባ ያሳሰቡት ፕ/ር በየነ፤ መድረኩ በአባላቱ ላይ እየደረሱ ነው ላለው በደል ድምፁን ከማሰማት ወደኋላ እንደማይል ገልፀዋል፡፡ አክለውም ከትናንት በስቲያ በደቡብ ክልል ሃዲያ ዞን የመድረክ አባል የሆነና በምርጫው ጉልህ
ተሣትፎ የነበረው አቶ ብርሃኑ ኤረቦ፣ ፖሊሶች ከቤት አስገድደው ከወሰዱት በኋላ ወንዝ ውስጥ
ሞቶ አስከሬኑ አርብ ጠዋት እንደተገኘ ፕ/ር በየነ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡

Published in ዜና
Page 7 of 16