በሰባት ዩኒቨርሲቲዎች ሊፈፀም የታቀደ የሙስና ወንጀልን መከላከሉን ጠቁሟል
የመከላከያ ሚኒስቴር 171ኛ ሬጅመንት መኮንኖች፤ ስኳር አውጥተው በመሸጥ ወንጀል ተከሰዋል

     የፀረ - ሙስና ኮሚሽን ባለፉት አስራ አንድ ወራት ውስጥ በህገወጥ መንገድ የተመዘበሩ ያላቸውን ከ81 ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ፣ ከ26ሺ ካሬ ሜትር በላይ የከተማ መሬት፣ አራት ህንፃዎች፣ ከ74 ሚሊዮን ብር በላይ ጥሬ ገንዘብና ሌሎች ንብረቶች ማስመለሱን ገለጸ፡፡ ኮሚሽኑ ባለፈው ሳምንት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው የአስራ አንድ ወር ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ እንደገለፀው፤ ከሙስና ወንጀል ጋር በተያያዘ ተፈፀሙ ባላቸው ጉዳዮች ላይ ምርመራ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ምርመራ ከተደረገባቸው የመንግስት ተቋማት መካከል ዩኒቨርሲቲዎች፣ ሆስፒታሎች፣ ባንኮች እና ጉምሩክ እንደሚገኙበትም በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሚካሄድ የህንፃ ግንባታ ሥራ በህገወጥ መንገድ ሊወጣ የነበረውን 135
ሚሊዮን ብር ማዳኑን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ በጅማ ዩኒቨርሲቲ፣ አምቦ፣ አዳማ፣ አርባምንጭ፣
ደብረማርቆስና ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲዎች ግልፅነት በሌላቸውና ከሥርዓት ውጪ የሆኑ አሰራሮችን
በመከተል ሊባክን የነበረ ከ645 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ማዳኑንም አመልክቷል፡፡ ኮሚሽኑ በመንግስት ትላልቅ ግዥና ሽያጭ ላይ ባደረገው ምርመራ፤ የመከላከያ ሚኒስቴር 171ኛ ሬጅመንት መኮንኖች፣ ከነጋዴዎች ጋር ተመሳጥረው ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ስኳር አውጥተው በመሸጥ ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸውን ጠቁሞ በወንጀሉ ተሳታፊ በሆኑ መኮንኖች ላይ ምርመራ ተደርጐ ክስ መመስረቱንም አስታውቋል፡፡ በሀሰተኛ የቀበሌ ነዋሪነት መሸኛ፣ መታወቂያና ውክልና የግለሰብ ቤትን 12 ሚሊዮን ብር የሸጡ ግለሰቦች፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ በሀሰተኛ ማስረጃ መሬት እንዲያገኙ የተደረጉ 89 ሰዎች፣ በአምስት
የግል ኩባንያዎች የተፈፀመ የ361.6 ሚሊዮን ብር የመንግሥት ታክስ አለመክፈል ወንጀል፣ በሁለት
አስመጪ ነጋዴዎች የተፈፀመና መንግስትን 301.9 ሚሊዮን ብር ገቢ ያሳጣ የሙስና ወንጀል፣ እንዲሁም በኢትዮቴሌኮም ሰራተኞችና በሌሎች የግል ሰራተኞች የተፈፀመና በመንግስት ላይ የ45 ሚሊዮን ብር ጉዳት ያደረሰ የሙስና ወንጀል ላይ ምርመራ አከናውኖ ክስ መመስረቱንም ኮሚሽኑበሪፖርቱ አስታውቋል፡፡    

Published in ዜና

ተቃዋሚዎች ውጤቱን አልተቀበሉትም

         በዘንድሮው አምስተኛ አገር አቀፍ ምርጫ፣ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የ442 ጣቢያዎችን ጊዜያዊ ውጤት ይፋ ማድረጉ የሚታወቅ ሲሆን በአገር አቀፍ ደረጃ መድረክ በሁለተኛነት፣ ሰማያዊ በሶስተኝነት ኢህአዴግን ይከተላሉ፡፡ በአዲስ አበባ የምርጫ ውጤት መሰረት፤ ሰማያዊ የሁለተኛነት፣ መድረክ ደግሞ የሦስተኝነት ደረጃ አግኝተዋል፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ ኢህአዴግ 26,007410 በማግኘት በአብላጫ ድምፅ ማሸነፉን የገለፀው ቦርዱ፤ መድረክ በ5መቶ 56ሺ 85 ሰማያዊ ፓርቲ በ3መቶ 79 ሺ 211 ድምፅ ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃን እንደያዙ ስታውቋል፡፡ መኢአድ አራተኛ፣ ቅንጅት አምስተኛ፣ ኢዴፓ ስድስተኛና አንድነት ሰባተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡
በአዲስ አበባ ኢህአዴግ 737ሺ 547 በማግኘት አብላጫውን ድምጽ ሲያሸንፍ፣ ሰማያዊ በ186ሺ 907 ድምፅ ሁለተኛ እንዲሁም መድረክ በ145ሺ 434 ድምፅ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል፡፡ የምርጫ ቦርድ የገለፀውን ጊዚያዊ ውጤት ተከትሎ መድረክ የዘንድሮ ምርጫ ከ2002 የባሰ የሀገሪቱን ዲሞክራሲ ያጨለመ ነው በማለት የምርጫውን ውጤት እንደማይቀበለው ሲገልፅ ሰማያዊ ፓርቲም፤ ምርጫው ኢ-ፍትሀዊ ፣ ወገንተኛ እና ተአማኒነት የሌለው በመሆኑ የምርጫውን ውጤት እንደማይቀበለው ገልጿል፡፡ አራተኛ ደረጃን ያገኘው መኢአድ፤ በምርጫው ወቅት አጋጠሙኝ ያላቸውን ችግሮች በመዘርዘር፣ የምርጫውን ውጤት እንደማይቀበል የገለፀ ሲሆን በስድስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኢዴፓም፤ ምርጫው ዲሞክራሲያዊ ፣ ፍትሀዊና በህብረተሰቡም ዘንድ ተአማኒ አልነበረም በማለት የምርጫውን ውጤት እንደማይቀበል አስታውቋል፡፡ በውጤቱ የአምስተኛ ደረጃን ያገኘው ቅንጅትና የሰባተኛ ደረጃን ያገኘው አንድነት የምርጫውን ውጤት በፀጋ እንደሚቀበሉ ገልፀዋል፡፡ ሄራዊ ምርጫ ቦርድ የተቃዋሚዎችን ክስ “መሰረተቢስ ውንጀላ ነው” ሲል ማጣጣሉ ይታወሳል፡፡

Published in ዜና

ከባለሙያው እውቀት ማነስ ወይም በሌላ ምክንያት በህክምና ላይ የሚፈጠሩ ስህተቶች ሊያጋጥሙ ይችላሉ፡፡ ሁሉም በህክምና ላይ የሚፈጠሩ ስህተቶች በባለሙያው የእውቀት ማነስ የሚከሰቱ ናቸው ማለት ባይቻልም የህክምና ባለሙያዎች ወቅታዊውን የህክምና ሳይንስ ባለማወቃቸው የተለያዩ የህክምና ስህተቶች ሲከሰቱ ይስተዋላል፡፡
እነዚህን በህክምና ላይ የሚከሰቱ ስህተቶች ለመቀነስ ብሎም የህክምና ባለሙያዎች በየጊዜው ከሚሻሻሉ የህክምና አሰራሮች ጋር እንዲተዋወቁ ለማድረግ CME (Continuous Medical Education) ወይም ቀጣይነት ያለው የህክምና ትምህርት በሚል በተለያየ የህክምና ስራ ላይ ላሉ ባለሙያዎች መሰጠት ከጀመረ ጥቂት አመታት ተቆጥረዋል፡፡
በዛሬው ፅሁፋችንም ይህን አይነቱ ስልጠና ለእራሳቸው ለባለሙያዎቹ እንዲሁም ለታካሚዎች የሚኖረው ጠቀሜታ በተጨማሪም ስልጠናውን በሀገራችን ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ምን ይመስላሉ የሚሉትን ጉዳዮች እንዳስሳለን፡፡
ይህ ቀጣይነት ያለው የህክምና ትምህርት የህክምና ባለሙያዎች እራሳቸውን በየግዜው ከሚሻሸለው የህክምና ሳይንስ ጋር እንዲተዋወቁ ለማድረግ የሚሰጥ ስልጠና ወይም ትምህርት እንደሆነ የፅንስና ማህፀን ሕክምና እስፔሻሊስት እና በኢትዮጵያ ፅንስና ማህፀን ሀኪሞች ማህበር የቦርድ አባል የሆኑት ዶክተር መንግስቱ ኃይለማሪያም ይናገራሉ፡፡
#...Continuous Medical Education ወይም CME የእንግሊዝኛ ቃል ሲሆን ትርጓሜውም ቀጣይነት ያለው የህክምና ትምህርት ማለት ነው፡፡ ይህ ቀጣይነት ያለው የህክምና ትምህርት መሰጠት ያስፈለገበት ዋነኛው ምክንያት የህክምና ሳይንስ በየጊዜው የሚለወጥና የሚቀያየር በመሆኑ የህክምና ባለሙያዎች በየጊዜው ከሚሻሻሉ የህክምና ሳይንሶች ጋር እንዲተዋወቁ እና ሙያቸውን እንዲያሻሽሉ ለማድረግ ነው፡፡ በተጨማሪም የህክምና አገልግሎት ተጠቃሚዎች ዘመናዊ የሆነ፣ ሳይንስ ያረጋገጠው እንዲሁም በመረጃ ላይ የተደገፈ አገልግሎት እንዲያገኙ እድል የሚፈጥር ተከታታይ የሆነ የትምህርት ሂደት ነው ማለት ነው፡፡”
ዶክተር መንግስቱ እንደገለፁት ቀጣይነት ያለው የህክምና ትምህርት በዋናነት የጤና ባለሙያዎች የሚሰጡት አገልግሎት ደረጃውን የጠበቀና ህብረተሰቡም ከዚህ ተጠቃሚ መሆኑን ለማረጋገጥ ታስቦ የሚሰጥ ሲሆን ያደጉ የሚባሉት ሀገራት ይህን አይነቱን ቀጣይነት ያለው የህክምና ትምህርት ስርአት ከጀመሩ ጥቂት አስርት አመታት እንደተቆጠሩ የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ባለሙያውም ይህንን ሀሳብ ያጋራሉ፡፡
“...ይህ አይነቱ ቀጣይነት ያለው የህክምና ትምህርት በብዙ ሀገሮች ላይ አለ፡፡ በተለይ ያደጉ የምንላቸው እና የህክምና አሰጣጥ ላይ ትልቅ ደረጃ የደረሱትን ሀገሮች ስንመለከት ይህን የስልጠና ስርአት ተግባራዊ ካደረጉ ቆይተዋል፡፡ በእነዚህ ሀገራት ከድሮ ጀምሮ ምናልባትም ከመቶ አመት ጀምሮ የጤና ባለሙያዎቻቸው በሚቆዩባቸው የስራ ግዜያት ውስጥ በየግዜው እራሳቸውን ማሻሻል እንደ ግዴታ የተቀመጠባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ በአሜሪካ ያለውን ሁኔታ ብንመለከት አንድ የጤና ባለሙያ ህጋዊ ሆኖ ለመስራት መውሰድ የሚገባው ኮርሶች አሉ፡፡ ስለዚህ ባለሙያው እነዛን ኮርሶች ወስዶ ማጠራቀም ያለበትን ነጥቦች ካላጠራቀመ የስራ ፍቃዱ አይታደስለትም፡፡ የስራፈቃዱ ደግሞ ካልታደሰ በሀገሪቱ ላይ መስራት አይችልም፡፡”
የስልጠና ስርአቱ የመጨረሻ ግብም የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች እጅግ ዘመናዊ ወይም ወቅታዊ የሆነ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ የጤና ባለሙያዎች ሙያቸውን የሚያሻሽሉበትን መንገዶች ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ ባለሙያው ይናገራሉ፡፡ በአሁኑ ሰአት ይህ ቀጣይነት ያለው የህክምና ትምህርት ሀገራችን ምን ደረጃ ላይ ይገኛል? የሙያ ማሻሻያ ስርአቱን ተግባራዊ ከማድረግ አንፃርስ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ምን ይመስላሉ?   ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥትውናል፡፡
“...ቀጣይነት ያለው የህክምና ትምህርት በሀገራችን ያለውን ታሪካዊ ዳራ ያየን እንደሆነ ይህ አይነቱ ስልጠና ኢትዮጵያ ውስጥ ኖሮ አያውቅም፡፡ በርካታ ባለሙያዎች ከየጤና ሳይንስ ኮሌጆቹ በየግዜው ይመረቃሉ፡፡ ከትምህርት ቤት ከወጡ በኋላም በየቦታው ይመደባሉ፡፡ ነገርግን የሚሰጡት አገልግሎት ተገቢ እና ደረጃውን የጠበቀ ነው ወይ? በሰለጠኑበት ሙያ የሚጠበቀውን አገልግሎት እየሰጡስ ነው ወይ? የሚለውን የምናረጋግጥበት መንገድ አልነበረም፡፡”
ነገር ግን የሙያ ማሻሻያ ስርአቱን ተግባራዊ ከማድረግ በጅምር ላይ ያሉ ስራዎች አሉ ይላሉ ባለሙያው፡፡
“...ቀደም ሲል እንደገለፅኩት ይህ አይነቱ የሙያ ማሻሻያ ስልጠና ሀገራችን አልነበረም፡፡ ነገር ግን ከአለፈው አመት ጀምሮ የጤና ጥበቃ ሚንስቴር በመድሀኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደር እና ቁጥጥር ባለስልጣን አማካኝነት የጀመረው ስራ አለ፡፡ በዚህም ሁሉም የህክምና ባለሙያዎች በተለይ ደግሞ የእስፔሻሊስት ሀኪሞች የሙያ ፈቃዳቸውን ለማደስ ከመምጣታቸው በፊት  በየአመቱ የተለያዩ ሙያዊ ትምህርቶችን በመውሰድ የተወሰኑ ነጥቦች ማጠራቀም ይኖርባቸዋል፡፡ ነገርግን ያንን ነጥብ ካላጠራቀሙ ፈቃዳቸው መታደስ የለበትም የሚል አካሄድ ተይዟል፡፡ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ታስቦ የነበረው ባለፈው መስከረም 2007 አመተ ምህረት ላይ ነበር፡፡ ነገርግን መመሪያው ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት መከናወን ያለባቸው ስራዎች አሉ፡፡  
ለምሳሌ በቅድሚያ ኮርሱን የሚሰጠውን ድርጅት ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ ትምህርቱን የሚሰጡት ዩንቨርሲቲዎች፣ በጤና ዙሪያ የሚሰሩ የሙያ ማህበራት ወይም ሌሎች በዚህ ጉዳይ ላይ ልምድ ያላቸው ተቋማት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ተቋማት ትምህርቱን ከመስጠታቸው በፊት ከሚመለከተው አካል ማለትም ከኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድሀኒትና ጤና ከብካቤ አስተዳደር እና ቁጥጥር ባለስልጣን ፍቃድ ማግኘት ይኖርባቸዋል፡፡ ስለዚህ መመሪያው በስራ ላይ ከመዋሉ በፊት እነዚህ ነገሮች ሁሉ መስተካከል ይኖርባቸዋል፡፡”  
በሀገራችን የጤና ባለሙያዎችን ምዝገባና የሙያ ፍቃድ አሰጣጥ ለመቆጣጠር በሚል የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድሀኒትና ጤና ከብካቤ አስተዳደር እና ቁጥጥር ባለስልጣን ተቋቁሞ በስራ ላይ ይገኛል፡፡
ባለሙያው እንደጠቀሱት ባለስልጣኑ ይህንን አይነቱን ቀጣይነት ያለው የህክምና ትምህርት ለመቆጣጠር በአዋጅ ቁጥር 661/2002 አንቀፅ 55 ንኡስ አንቀፅ እና ደንብ ቁጥር 299/2006 መሰረት የጤና ባለሙያዎች የሙያ ስራ ፈቃድ አሰጣጥ አስተዳደር እና ቁጥጥር መመሪያ አውጥቶ  ተግባራዊ ለማድረግ በስራ ላይ ይገኛል፡፡
ባለስልጣኑ ባወጣው መመሪያ መሰረት “ተከታታይ የሙያ ማጎልበቻ” ማለት ማንኛውም የጤና ባለሙያ በስራ ላይ እያለ በሙያው ያገኘውን እውቀት እና ክህሎት ጠብቆ እንዲቆይ እና የሙያ ብቃቱን ለማጎልበት በየግዜው የሚወስደው ስልጠናና ሌሎች የሙያ ማጎልበቻ ስራዎችን እንደሚያካትት ተገልፆአል፡፡
መመሪያውን ማውጣት ያስፈለገበት ዋና አላማም፡-
የጤና ባለሙያዎችን ምዝገባና የሙያ ስራ ፈቃድ አሰጣጥ አስተዳደርና ቁጥጥር ስርአትን በማጠናከር የህብረተሰቡን ደህነት ለመጠበቅ
ህብረተሰቡ ሙያዊና ስነ ምግባራዊ ብቃት ባላቸው የጤና ባለሙያዎች አገልግሎቱን እንዲያገኝ ለማስቻል እንዲሁም
የጤና ባለሙያዎች ምዝገባና  የሙያ ስራ ፈቃድ አሰጣጥ አስተዳደር እና ቁጥጥር ስራ በግልፅነትና ተጠያቂነት ስርአት እንዲፈፀም ለማድረግ ነው፡፡
በሚል በዝርዝር ተቀምጧል፡፡  
እንደ ባለሙያው ከሆነ ትምህርቱ በክፍል ውስጥ፣ በኢንተርኔት ወይም በተለያየ ግዜ በሚደረጉ የሙያ ማህበራት አመታዊ ስብሰባዎች ላይ ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ የሙያ ማህበራት አመታዊ ስብሰባዎች በተወሰነ የህክምና ዘርፍ ላይ ያሉ የህክምና ባለሙያዎች ህብረት በመሆኑ በዘርፉ የሚኖሩ ለውጦችን ለባለሙያዎች ለማሳወቅ አይነተኛ መንገድ ነው፡፡ በዚህም በሙያው ዙሪያ ያሉ የተለያዩ ጥናታዊ ፅሁፎች ይቀርባሉ በተጨማሪም በሙያው ላይ ያሉ አዳዲስ አሰራሮችም ይተዋቃሉ፡፡
አዲስ በወጣው መመሪያ መሰረት የጤና ባለሙያዎች እንደዚህ አይነት የሙያ ማሻሻያ ትምህርቶችን ተከታትሎ መውሰድ እና የሙያ ፈቃዳቸውን ለማደስ የሚያስችላቸውን ነጥብ በተገቢው ግዜ አሟልተው መገኘት እንዳለባቸው ተጠቅሷል፡፡
ስለዚህም ይላሉ ዶክተር መንግስቱ፡-
“..ስለዚህ ዋናው ነገር እያንዳንዱ የጤና ባለሙያ ከሙያው ጋር የተገናኘውን ኮርስ መውሰድ አለበት፡፡ ለምሳሌ የማህፀንና ፅንስ ሀኪሞች መውሰድ ያለባቸው ከሙያው ጋር የሚገናኝ ኮርስ ነው፡፡ ነገርግን ትምህርቱን ከመውሰዳቸው በፊት ስልጠናውን የሚሰጠው ተቋም ከሚመለከተው የመንግስት አካል እውቅና የተሰጠው መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን አጠቃላይ የስልጠና ሂደቱ የተቀናጀ አይነት አካሄድ ላይኖረው ይችላል፡፡”
ይቀጥላል

Published in ላንተና ላንቺ

 ለ60ኛዋ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ  የስፔንና የጣሊያን ሻምፒዮኖቹ ባርሴሎናና ጁቬንትስ ይፋጠጣሉ፡፡ ሁለቱ ክለቦች በአገሮቻቸው የውስጥ ውድድር ሁለት ሁለት ዋንጫን በመውሰዳቸውና በሻምፒዮንስ ሊጉም ከፍተኛ ብቃት አሳይተው ለፍፃሜ በመድረሳቸው ዋንጫውን ማን እንደሚወስድ ለመገመት አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ ጁቬንትስ  ከ12 ዓመታት በኋላ ለሻምፒዮንስ ሊግ የዋንጫ ጨዋታ በመቅረብ  ለ3ኛ ጊዜ እንዲሁም ባርሴሎና ባለፉት 10 ዓመታት 4 የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን ካነሳ በኋላ  ለ5ኛ ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒዮን ለመሆን ያነጣጥራሉ፡፡
የፍፃሜውን ጨዋታ በኦሎምፒያ ስታድዬን ተገኝቶ ለማየት የትኬት ዋጋ ከ70  ጀምሮ 160 ፤ 280 እና 390 ዩሮ ሲሆን፤ በ200 አገራት እስከ 180 ሚሊዮን የቲቪ ተመልካች ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ዋንጫውን የሚያሸንፈው ክለብ 10.5 ሚሊዮን ዩሮ ተሸናፊው ደግሞ 5.5 ሚሊዮን ዩሮ የሽልማት ገንዘብ ከአውሮፓ እግር ኳስ የሚበረከትለት ሲሆን፤ ዋንጫው አሸናፊ አጠቃላይ ገቢው በሽልማት ገንዘብ፤ በቲቪ ስርጭት መብት እና በሌሎች የገቢ ድርሻዎች እስከ 35 ሚሊዮን ዩሮ ይሆናል፡፡ በፍፃሜው ፍልሚያ ጁቬንትስ ባርሴሎና ዋና ማልያቸውን የመልበስ ዕድል አግኝተዋል፡፡ በቀድሞዎቹ የሻምፒዮንስ ሊግ የዋንጫ ጨዋታዎች ክለቦች ዋና ማልያቸውን የመልበስ ዕድል ማግኘታቸው የተለመደ አልነበረም፡፡ ባርሴሎና ሰማያዊና ቀይ ሸንተረር ሹራብ፣ ከሰማያዊ ቁምጣና ቀይ ገምባሌ ጋር ሲታጠቅ፤ ጁቬንትስ ደግሞ ጥቁርና ነጭ ሸንተረር ሹራብ ነጭ ቁምጣ እና ነጭ ገምባሌ በመልበስ ይሰለፋል፡፡ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የኮከብ ግብ አግቢነት ፉክክር የባርሴሎናው ሊዮኔል ሜሲ እና የሪያል ማድሪዱ ክርስትያኖ ሮናልዶ በእኩል 10 ጐሎች ተያይዘዋል፡፡ በሌላ በኩል በሻምፒዮንስ ሊግ የምንግዜም ከፍተኛ ግብ አግቢ ደረጃ ሊዮኔል ሜሲ ከክርስትያኖ ሮናልዶ ጋር በእኩል 77 ጎሎች እየተፎካከሩ ሲሆን በዋንጫ ጨዋታው ሊዮኔል ሜሲ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ ለመጨረስና የምንጊዜም ከፍተኛ አግቢነቱን በብቸኝነት ለመቆጣጠር ዕድል ይኖረዋል፡፡
የባርሳው አሰልጣኝ ሊውስ ኢነሪኬ በ2014 እኤአ ላይ ቡድኑን ከፔፔ ጋርዲዮላ ሲረከብ በታክቲክ ረገድ ፈተና ቢገጥመውም  በዘንድሮ የውድድር ዘመን ግን ከቡድኑ ጋር ልዩ ውህደት ፈጥሮ ጠንካራ ቡድን መገንባት ችሏል፡፡ ኤነሪኬ በውድድር ዘመኑ የኮፓ ዴላሬይ እና የላሊጋውን የሻምፒዮናነት ክብሩን ማግኘቱም ለክለቡ የፍፃሜ ፍልሚያ አበረታች ሁኔታን ፈጥሮለታል፡፡ በተለይ የባርሳን ተከላካይ መስመር በከፍተኛ ደረጃ ባጠናከረበት ስልጠናው እየተደነቀም ነው፡፡ ባርሴሎና በሻምፒዮንስ ሊጉ የፍፃሜ ጉዞው በብዙ ጨዋታዎች የኳስ ቁጥጥሩን እስከ 60 በመቶ በማድረግ ያሳየው ብልጫ እና በቡድን ስብስቡ ያለው ልምድ ከጁቬንትስ የተሻለ ግምት እንዲሰጠው ምክንያት ሆኗል፡፡
ከአውሮፓ ውድድሮች ርቀው የነበሩትን የጣሊያን ክለቦች ያነቃቃው የጁቬንትስ የዋንጫ ግስጋሴ የማይናቅ ተፎካካሪ መሆኑን ያሳይለታል፡፡ በማሲሞ አሌግሪ የሚመራው የጁቬንትስ ቡድን ልምድ ባካበቱ ተጨዋቾቹም ከመጠቀሱም በላይ በተለይ በአማካይ መስመር ባለው ጥንካሬ ከባርሴሎና የተሻለ መሆኑ ግምት ያሰጠዋል፡፡ በመልሶ ማጥቃት አጨዋወቱም ከባርሳ የተሻለ ብቃት ማሳየቱን የውድድር ዘመኑ ሲያመለክት ቆይቷል፡፡ የጁቬንትሱ አሰልጣኝ ማሲሚላኖ አሌግሪ በተለይ በሁለት ተጨዋቾቻቸው ልዩነት መፍጠር እንደሚቻል ተማምነዋል፡፡ በአውሮፓ ውድድሮች ከፍተኛ ልምድ የያዘው እና ዘንድሮ ጁቬ ዋንጫ እንዲያገኝ ከፍተኛ አስተዋፅኦ የነበረው ካርሎስ ቴቬዝ እና ከጉዳት በፍጥነት አገግሞ ለዋንጫ ጨዋታው የተመለሰው አርተር ቪዳል ናቸው፡፡ በ2006 እኤአ ዓለም ዋንጫን በጣልያን ብሄራዊ ቡድን ያሸነፉት አንድሬ ፒርሎ እና ጂያንሉጂ ቡፎንም ከፍተኛ ሚና እንደሚኖራቸው ተገምቷል፡፡
በማጥቃት ላይ በተመሰረተ ጨዋታ እና በጎሎች የደመቀ የዋንጫ ጨዋታ በተመልካች ይወደዳል፡፡ ባርሴሎና ጁቬንትስ በተጨዋች ስብስባቸው ይህን ፉክክር እንደሚያሳዩ ተጠብቀዋል፡፡ በተለይ ባርሴሎና በሶስቱ ደቡብ አሜሪካውያን ሊዬኔል ሜሲ፤ ኔይማር እና ስዋሬዝ ጥምረት በጎል ሊንበሻበሽ ይችላል፡፡ ሶስቱ ተጨዋቾች ዘንድሮ በሁሉም ውድድሮች 120 ጎሎች አስመዝግበዋል፡፡ በእግር ኳስ ታሪክ በአጥቂ መስመር የተመዘገበ ከፍተኛው የጎል ብዛት ነው፡፡ አስቀድሞ የተመዘገበው ሪከርድ በ2012 ሮናልዶ፤ ሄጊዌን እና ቤንዜማ ያስቆጠሩት 118 ጎሎች ነበር፡፡ ሊዮኔል ሜሲ በውድድር ዘመኑ ብቻውን 58 ጎሎች ሲያገባ 27 ጎል የበቁ ኳሶችን አቀብሏል፡፡ ስዋሬዝ ለባርሴሎና ባደረጋቸው 36 ግጥሚያዎች 24 ጎሎች እንዲሁም 17 ለጎል የበቁ ኳሶች አቀብሏል፡፡ ኔይማር ደግሞ 44 ጨዋታዎች ተሰልፎ 39 ጎሎች እና 7 ጎል የሆኑ ኳሶች መስራት ችሏል፡፡ ስለዚህም በዛሬው ምሽት የፍፃሜ ጨዋታ ከእነዚህ ሶስት ተጨዋቾች ቢያንስ ሁለት ጎል መጠበቅ ላይከብድ ይችላል፡፡ በአንፃሩ ግን ጁቬንትስ እንደ ባርሴሎና አስፈሪ የአጥቂ መስመር የለውም፡፡ ክለቡ በጣሊያን ውስጥጭ ውድድሮች ያገባው 72 ጎሎች ብቻ ሲሆን ከአጥቂ መስመር ተሰላፊዎቹ አንዳቸውም ከ30 ጎሎች በላይ አላስመዘገቡም፡፡ የቡድኑ ፊትአውራሪ ሊባል የሚቻለው ካርሎስ ቴቬዝ በአገር ውስጥ ውድድሮች 29 እንዲሁም በሁሉም ውድድሮች 29 ጎሎችና  8 ጎል የሆኑ ኳሶች አቀብሏል፡፡ ሌላው የጁቬንትስ አጥቂ መስመር አለኝታ ሊሆን የሚችለው በአየር ላይ ከፍተኛ ብቃት ያለው ግዙፉ ፈርናንዶ ሎርዬንቴ ነው፡፡ ሎርዬንቴ ዘንድሮ ለክለቡ 39 ጨዋታዎች አድርጎ ያገባው 9 ጎሎች ቢሆንም በዋንጫ ጨዋታው ከቴቬዝ ጋር በሚኖረው ጥምረት ለባርሴሎና ተከላካይ መስመር ብዙ ስጋቶችን መፍጠሩ የማይቀር ይሆናል፡፡ የ22 ዓመቱ ጣሊያናዊ አልቫሮ ሞራቶ እና ፈረንሳዊው ፖል ፖግባም አማራጮች ናቸው፡፡
ለዋንጫዎች ሃትሪክ
በ2014/15 ባርሴሎናና ጁቬንትስ በየአገራቸው 2 ዋንጫዎችን እያንዳንዳቸው ወስደዋል፡፡ ለአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ የሚፋለሙት የውድድር ዘመኑን በዋንጫ ሃትሪክ ለመደምደም ይሆናል፡፡ በስፔን ላሊጋ ሻምፒዮን ለመሆን የበቃው ባርሴሎና በተጨማሪ የኮፓ ዴላሬይን ዋንጫ የወሰደ ሲሆን ጁቬንትስ ደግሞ የሴሪኤውን የስኩዴቶ ክብር ካስመዘገበ በኋላ ሁለተኛውን ዋንጫ በኮፓ ኢታሊያ ተጐናጽፏል፡፡
12 አገራት የተወከሉበት ፍፃሜ
በሁለቱ ቡድኖች የተጨዋቾች ስብስብ በሻምፒዮንስ ሊጉ የዋንጫ 12 አገራት የሚወከሉ ይሆናል፡፡ በጁቬንትስ እና በባርሴሎና 50 ተጨዋቾች 14 ከጣሊያን፤ 13 ከስፔን፤ 5 ከብራዚል፤ 4 ከአርጀንቲና እና ፈረንሳይ፤ 2 ከኡራጋይ፤ ቺሊና ክሮሽያ እንዲሁም 1 ከቤልጅዬም ከጀርመን ከሴኔጋል እና ስዊዘርላንድ የተወከሉ ናቸው፡፡ የጁቬንትስ 25 ተጨዋቾች ከ8 አገራት የተወከሉ ናቸው፡፡ 14 ከጣሊያን፤ 3 ከፈረንሳይ፤ 2 ከአርጀንቲና እና ከስፔን እንዲሁም 1 ከብራዚል ከቺሊ ስዊዘርላንድ እና ኡራጋይ ናቸው፡፡ የባርሴሎና 25 ተጨዋቾች ደግሞ ከ10 አገራት የተውጣጡ ናቸው፡፡ 11 ከስፔን፤ 4 ከብራዚል፤ 2 ከአርጀንቲና እና ከክሮሽያ እንዲሁም 1 ከቤልጅዬም ከቺሊ ከጀርመን ፈረንሳይ ሴኔጋል እና ኡራጋይ ተሰብስበዋል፡፡
ስፔን 14 ጣሊያን 12
በ60ኛዋ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የፍፃሜ ፍልሚያ የስፔን ክለቦች 14 እንዲሁም የጣሊያን ክለቦች 12 ዋንጫዎች በመውሰድ ቀርበዋል፡፡ ስፔን በሁለት ክለቦች ለ14 ጊዜያት (10 በሪያልማድሪድ፣ 4 በባርሴሎና) ዋንጫውን ስትወስድ፣ ጣሊያን ደግሞ በ3 ክለቦች ለ12 ጊዜያት (ኤሲሚላን 7፣ ኢንተርሚላን 3 እና ጁቬንትስ 2) ዋንጫዎችን ተቀዳጅተዋል፡፡  የጣሊያንና የስፔን ክለቦች በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት በ1998 እ.ኤ.አ ሲሆን ሪያልማድሪድ ጁቬንትስን 1ለ0 በማሸነፍ ተሳክቶለታል፡፡
በሻምፒዮንስ ሊግ ገድሎችና ዋንጫዎች ስብስብ
በጀርመን ዋና ከተማ በርሊን ውስጥ በሚገኘው ኦሎምፒያታድዬን ሁለቱ ክለቦች ለአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ ሲቀርቡ እኩል ስምንት ጊዜ ነው፡፡ በ8 ዋንጫ ጨዋታዎች ባርሴሎና አራት ጊዜ ዋንጫውን ሲወስድ ጁቬንትስ ደግሞ ሁለቴ የአውሮፓን ንግስና ማግኘት ችሏል፡፡ ጁቬንትስ ሁለቱን የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎች የወሰደው በ1985 እ.ኤ.አ የእንግሊዙን ሊቨርፑል እንዲሁም በ1998 እ.ኤ.አ የሆላንዱን አያክስ በማሸነፍ ነበር፡፡ በሌሎች 5 ጊዜያት ለዋንጫ ጨዋታ ቀርቦ በሆላንዱ አያክስ፣ በጀርመኖቹ ሃምበርግና ዶርቱመንድ፣ በስፔኑ ሪያል ማድሪድና በጣልያኑ ኤሲሚላን በመሸነፍ የአውሮፓን ክብር ሳይገኝ ቀርቷል፡፡
በሌላ በኩል ባርሴሎና በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ያገኛቸውን 4 ዋንጫዎች በ1992 ኤሲሚላንን በ2006 እ.ኤ.አ አርሰናልን በ2009 እ.ኤ.አ ማንቸስተር ዩናይትድን በ2011 እ.ኤ.አ ባየር ሙኒክን ማሸነፍ ነበር፡፡ ባርሴሎና የተሸነፈው በ1960 በቤነፊካ፤ በ1985 በስታዎ ቡካሬስት እንዲሁም በ1993 በኤሲሚላን ክለቦች ነው፡፡
የስፔኑ ክለብ ባርሴሎና በውድድር ታሪኩ አራት የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን ብቻ ሳይሆን  27 የላሊጋ ፤ 26 የስፓኒሽ ካፕ ኮፖዴለሬይን ፤ እንዲሁም ተጨማሪ 13 ዋንጫዎችን በአውሮፓ እና በሌሎች ዓለም አቀፍ ውድድሮች አስመዝግቧል፡፡ የጣሊያኑ ክለብ ጁቬንትስ ደግሞ ለ2 ጊዜያት የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ከማሸነፉ በተጨማሪ ለ31 ጊዜ የሴሪኤውን የስኩዴቶ ክብር፣ 11 ጊዜ የኮፓ ኢታሊያን ዋንጫዎችን ሰብስቧል

ማነፃፀሪያ                                 ጁቬንትስ                                   ባርሴሎና
የተጨዋቾች አማካይ ዕድሜ        29.2 ዓመት                            26.8
የሌላ አገር ተጨዋቾች ብዛት          12                                              13
የብ ቡድን ተጨዋቾች ብዛት          19                                              16
ስታድዬም                                ዴላልፒ 41,011 ተመልካች           ኑካምፕ 99,304
አጠቃላይ የቡድን ዋጋ ግምት         318.70 ሚ.ዩሮ                             591.50 ሚ.ዩሮ
ዓመታዊ ገቢ                         279.40 ሚ.ዩሮ                             484.6 ሚ.ዩሮ
የጨዋታ ቀን ገቢ (በዓመት)         41 ሚ.ዩሮ                                116.8 ሚ.ዩሮ
ዓመታዊ የቲቪ ገቢ                         153.4 ሚ.ዩሮ                             182.1 ሚ.ዩሮ
ዓመታዊ የንግድ ገቢ                         85.ሚ.ዩሮ                             155.3 ሚ.ዩሮ
የአሰልጣኞች ደሞዝ (በዓመት)        አሌግሪ 2ሚ.ዩሮ                        ኢነርኬ 5.5 ሚ.ዩሮ
ከፍፃሜው በፊት ያገኙት ገቢ            24.4 ሚ.ዩሮ                             25.9 ሚ.ዩሮ
የምርጥ 11 ዋጋ                            119.7 ሚ.ዩሮ                             248.5 ሚ.ዩሮ
አጠቃላይ የክለብ ዋጋ ተመን               774 ሚ.ዩሮ                             2.9 ቢ ዩሮ

የ2007 የኢትዮጵያ ፕሪሜሪሊግ ኮከብ ተጫዋች የሆነው የቅዱስ ጊዮርጊሱ በኃይሉ አሰፋ በብሄራዊ ቡድን ደረጃም ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ይጠበቃል፡፡  
   
   ዋልያዎቹ ከሳምንት በኋላ ለ2017 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታ በሜዳቸው ከሌሶቶ ጋር የሚገናኙ ሲሆን፤ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ለመጨረሻው ዝግጅት የመረጧቸውን  24 ተጨዋቾች ዝርዝር በሳምንቱ አጋማሽ ላይ አስታውቀዋል፡፡ ከውጭ ሀገር ክለቦች ከተጠሩት ተጨዋቾች መካከል ዋሊድ አታ በጉዳት ምክንያት መሰለፍ እንደማይቻል  ፌደሬሽኑ ቢገለጽም፤ ከፍተኛ ልምድ ያላቸውና  ቡድኑን ወሳኝ ተጨዋቾች የሆኑት እነ ሳላዲን ሰኢድ፣ ሽመልስ በቀለ፣ አዲስ ህንፃና ጌታነህ ከበደ መቼ እንደሚቀላቀሉ አላስታወቀም፡፡  በሌላ በኩል ለመጨረሻ ዝግጅት 24 ተጨዋቾችን የያዘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን  ከዛምቢያ ብሄራዊ ቡድን ጋር  ለወዳጅነት ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታድየም እሁድ እንደሚጫወት ሲታወቅ ትናንት አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡
የዛምቢያ ብሄራዊ ቡድን በኮሳፋ ካፕ ለፍፃሜ ደርሶ በማላዊ ዋንጫውን ቢነጠቅም የቡድኑ አሰልጣኝ ኦነር ጃንዛ ስብሰባቸው ለአፍሪካ ዋንጫ ብቻ ሳይሆን በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ለዓለም ዋንጫ ለመብቃትም እንደሚሰራ ሰሞኑን ለሱፕር ስፖርት ተናግረዋል፡፡ በ2017 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ከሳምንት በኋላ ዋልያዎቹ ከሌሶቶ  ሲገናኙ ዛምቢያ  ጊኒ ቢሳዎን በመጀመርያ ጨዋታ በሜዳዋ ታስተናግዳለች፡፡
ኢትዮጵያ እና ዛምቢያ ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት በ2013 እኤአ ደቡብ አፍሪካ አዘጋጅታ በነበረው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ ነበር፡፡ በወቅቱ በምድብ 3 የመጀመርያ ጨዋታ ሩስተንበርግ ላይ ተገናኝተው 1 እኩል አቻ መለያየታቸው ይታወሳል፡፡ በወቅቱ ለዛምቢያ ጎል ያስቆጠረቅ ኮሊንስ ሜብሱማ ሲሆን ኢትዮጵያን አቻ ያደረገው ደግሞ አዳነ ግርማ ነበር፡፡

     ለመጨረሻው ዝግጅት የተመረጡት  የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች ዝርዝር
ግብ ጠባቂዎች

የተጨዋች ስም          ክለብ    
ታሪክ ጌትነት     ደደቢት     
ጀማል ጣሰው     መከላከያ     
አቤል ማሞ     ሙገር ሲሚንቶ    

ተከላካዮች  
የተጨዋች ስም    ክለብ    
ስዩም ተስፋዬ    ደደቢት     
ሞገስ ታደሰ     ሲዳማ ቡና      
አስቻለው ታመነ      ደደቢት     
ሙጂድ ቃሲም     ሐዋሳ ከነማ    
ተካልኝ ደጀኔ     ደደቢት     
ዘካሪያስ ቱጂ    ቅ/ጊዮርጊስ     
ሳላዲን በርጌቾ    ቅ/ጊዮርጊስ     
ግርማ በቀለ    ሐዋሳ ከነማ    
በረከት ቦጋለ    አርባ ምንጭ ከነማ    

የመሀል ሜዳ ተጨዋቾች  
የተጨዋች ስም    ክለብ    
ራምኬል ሎክ     ኢትዮ. ኤሌክትሪክ     
አስቻለው ግርማ    ኢትዮጵያ ቡና     
ብሩክ ቃልቦሬ    ወላይታ ድቻ    
ጋቶች ፖኖም    ኢትዮጵያ ቡና     
ምንተስኖት አዳነ    ቅ/ጊዮርጊስ     
በኃይሉ አሰፋ    ቅ/ጊዮርጊስ    
ፍሬው ሰለሞን     መከላከያ    
ኤፍሬም አሻሞ    ንግድ ባንክ     

አጥቂዎች   
የተጨዋች ስም     ክለብ     
ባዬ ገዛኸኝ     ወላይታ ድቻ    
ኤፍሬም ቀሪ    ሙገር ሲሚንቶ    
ዮናታን ከበደ    አዳማ ከነማ    
ቢኒያም አሰፋ    ኢትዮጵያ ቡና     

ሩስያ መጠነ ሰፊ ወረራ ልታደርግብን ትችላለች ብለዋል

   በሩስያ በሚደገፉት የዩክሬን አማጽያን እና በመንግስት ጦር መካከል ባለፈው ረቡዕ የከፋ ግጭት መከሰቱን ተከትሎ፣ ፕሬዚደንት ፔትሮ ፖሮሼንኮ የጦር ሃይላቸው ከሩስያ ሊቃጣ ከሚችል የተደራጀ መጠነ ሰፊ ወረራ አገሪቱን ለመከላከል በተጠንቀቅ እንዲቆም ማሳሰባቸውን ሮይተርስ ዘገበ።
የሩስያ ወታደሮች ከዩክሬን አማጽያን ጋር በመተባበር በምስራቃዊ የአገሪቱ ክፍል ጥቃት እየፈጸሙ ነው ሲሉ ከትናንት በስቲያ ለአገሪቱ የፓርላማ አባላት የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፣ ጦራቸው ከአማጽያኑ የሚቃጣበትን ጥቃትና ከሩስያ ጋር በሚያዋስኗት ሁሉም የድንበር አካባቢዎች ሊፈጸምበት ከሚችለው ሰፊ ወረራ አገሪቱን ለመከላከል በበቂ ሁኔታ መዘጋጀት ይኖርበታል ብለዋል፡፡
የዩክሬን አማጽያን ባለፈው ረቡዕ ማሪንካ ከተማን ለመቆጣጠር ባደረጉት ሙከራ፣ ከመንግስት ጦር ጋር በከባድ የጦር መሳሪያዎች የታገዘ አስከፊ ግጭት መደረጉን የጠቆመው ዘገባው፣ ፕሬዚዳንቱም ግጭቱ ሩስያና አማጽያኑ በአገሪቱ ላይ ቀጣይ የተደራጀ ወታደራዊ ጥቃት እንደሚሰነዘር የሚያሳይ ነው ማለታቸውን ገልጧል፡፡
ዩክሬንና የኔቶ አባል አገራት የሆኑ አጋሮቿ፣ በአገሪቱ ምስራቃዊ አካባቢዎች የሚገኙ ሁለት ግዛቶችን ከፊል አካባቢዎች ይዘው ለሚገኙት አማጽያን የጦር መሳሪያዎችንና ወታደሮችን በመላክ ጥቃት እየፈጸመች ነው ሲሉ ሩስያን በተደጋጋሚ ሲከሱ መቆየታቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ባለፈው የካቲት ወር ላይ የተኩስ አቁም ስምምነት ቢደረስም፣ መጠነኛ ግጭቶች ሲከሰቱ መቆየታቸውንና፣ ባለፈው ረቡዕም አስከፊ የተባለው ግጭት መከሰቱን ገልጧል፡፡ ምዕራባውያን አገራት ሩስያ በሰላም ስምምነቱ ውስጥ የተካተቱ ሃላፊነቶቿን አልተወጣችም ሲሉ የተቹ ሲሆን፣ ወታደሮቿን ከዩክሬን ግዛት ማስወጣትና ለአማጽያኑ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ማድረጓን ማቆም አለባት ማለታቸውን ዘገባው አስረድቷል፡፡
ሩስያ በበኩሏ፤ ግጭቱን እንደገና የቆሰቆሰችው ዩክሬን ናት፣ ይህንንም ያደረገችው በቅርቡ በሩስያ ላይ የኢኮኖሚ ማዕቀብ ይጣል አይጣል የሚለውን ይወስናል ተብሎ በሚጠበቀው የአውሮፓ ህብረት ላይ ጫና ለማሳደር በማሰብ ነው ብላለች፡፡
ፕሬዚዳንት ፖሮሼንኮ በአሁኑ ወቅት 9ሺህ ያህል የሩስያ ወታደሮች ድንበር ጥሰው ገብተው በግዛታችን ወታደራዊ እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው ቢሉም፣ ሩስያ በበኩሏ መሰረተቢስ ውንጀላ ነው ስትል የፕሬዚዳንቱን ንግግር ማጣጣሏን ዘገባው ጠቁሟል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከአጠቃላይ አገራዊ ምርቷ 5 በመቶውን ለወታደራዊ በጀት የመደበችው ዩክሬን፣ በቀጣዩ አመትም በወታደራዊ በጀቷ ላይ ጭማሪ ልታደርግ እንደምትችል ፕሬዚዳንት ፖሮሼንኮ ለፓርላማ አባላቱ ባደረጉት ንግግር መግለጻቸውንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

የብሩንዲው ፕሬዚዳንት ፔሪ ንኩሩንዚዛ ህገመንግስቱ ከሚፈቅድላቸው ውጪ ለሶስተኛ ዙር በምርጫ ለመወዳደር መወሰናቸውን ተከትሎ በአገሪቱ የተቀሰቀሰው ግጭት በዚህ ሳምንትም ያገረሸበት ሲሆን  የአገሪቱ የፓርላማና ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለሶስተኛ ጊዜ ዳግም መራዘሙን ቢቢሲ ዘገበ፡፡ በአገሪቱ ያለው ሁኔታ ሰላማዊ ምርጫን ለማከናወን አያስችልም በሚል ምርጫውን እንዲያራዝሙ ከአፍሪካውያንና ምእራባውያን መንግስታት ጫና ሲደረግባቸው የቆዩት ፕሬዚዳንቱ፣ ምርጫው እንዲራዘምና በመጪው ነሃሴ ወር መጨረሻ እንዲካሄድ መወሰናቸውን ከትናንት በስቲያ አስታውቀዋል፡፡
ከአገሪቱ ዋነኛ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች አንዱ የሆኑት አጋቶን ሩዋሳ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፣ ፕሬዚዳንት ንኩሩንዚዛ አምባገነን መሪ ስለሆኑ ከስልጣናቸው መውረድ አለባቸው ያሉ ሲሆን፣ የጸጥታ ሁኔታው ሳይሻሻል፣ ገለልተኛ የምርጫ ኮሚሽን ሳይመረጥና የግል ሚዲያው ላይ የሚደረገው ጫና ሳያበቃ በአገሪቱ ምርጫ ሊከናወን አይችልም ብለዋል፡፡ የብሩንዲ ምርጫ ከዚህ ቀደም እንዲራዘም በተወሰነው መሰረት፣ የፓርላማ ምርጫው ትናንት፣ የፕሬዚዳንታዊ ምርጫው ደግሞ በሰኔ ወር መጨረሻ ሊካሄድ ቀን ተቆርጦ ነበር፡፡
ፕሬዚዳንቱ በምርጫ ለመወዳደር መወሰናቸውን ማስታወቃቸውን ተከትሎ ያልተሳካ መፈንቅለ መንግስት መካሄዱና በአገሪቱ በተቀሰቀሰው ግጭት ከ20 በላይ ዜጎች መሞታቸውን፣ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ብሩንዲያውያንም ወደ ጎረቤት አገራት መሰደዳቸውን ባለፈው ሳምንት መዘገባችን ይታወሳል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

 አሸናፊው ሮቦት 3.5 ሚሊዮን ዶላር ይሸለማል

    በሮቦቲክስ መስክ የተሰማሩ 24 የአለማችን ኩባንያዎችና የምርምር ቡድኖች ያመረቷቸው ሮቦቶች የተሳተፉበትና 3.5 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት የሚያስገኘው የዳርፓ የሮቦቶች ውድድር ትናንትና ዛሬ በአሜሪካ እየተካሄደ እንደሚገኝ ቢቢሲ ዘገበ፡፡
በአሜሪካው መከላከያ ቢሮ ፔንታጎን ድጋፍ በሎሳንጀለስ አቅራቢያ በመከናወን ላይ በሚገኘው በዚህ ውድድር የሚሳተፉ ሮቦቶች አደጋን የመቋቋም ብቃታቸውን የሚያሳዩ አስቸጋሪ ተግባራትን እንዲፈጽሙ በማድረግ አሸናፊው ይለያል ተብሏል፡፡
ሮቦቶቹ እንዲያከናውኗቸው ከተመደቡላቸው ስምንት ተግባራት መካከል፡- መኪና መንዳት፣ በር መክፈትና ማለፍ፣ ግድግዳ መብሳት፣ በደረጃዎች ላይ መወጣጣት የሚገኙበት ሲሆን፣ በውድድሩ ላይ የሚገለጽ ሌላ ለየት ያለ ተልዕኮም እንዲፈጽሙ ይደረጋል፡፡
እያንዳንዱ ሮቦት እነዚህን ስምንት ተግባራት ለማከናወን ሁለት ሙከራዎች የሚሰጡት ሲሆን ፈጥኖ ተግባራቱን በተሳካ ሁኔታ ማከናወንም ለአሸናፊነት በመስፈርትነት ከተቀመጡት ነጥቦች አንዱ እንደሆነ ዘገባው ጠቁሟል፡፡
የውድድሩ አዘጋጅ የሆኑት ዶክተር ጊል ፕራት እንዳሉት፣ የዘንድሮው ውድድር ከአምናው ጋር ሲነጻጸር በአስር እጥፍ አስቸጋሪ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የተለያዩ የአለም አገራት የሮቦቲክስ ዘርፍ ኩባንያዎችና የምርምር ቡድኖች ለውድድሩ የቀረቡ ቢሆንም፣ የመጀመሪያውን ማጣሪያ አልፈው ለፍጻሜ የደረሱት፣ 24 መሆናቸውንና ከእነዚህም መካከል የአሜሪካ፣ የደቡብ ኮርያ፣ የጃፓን፣ የጀርመንና የጣሊያን ኩባንያዎች እንደሚገኙበት ዘገባው አመልክቷል፡፡  

Published in ከአለም ዙሪያ

የብሩንዲው ፕሬዚዳንት ፔሪ ንኩሩንዚዛ ህገመንግስቱ ከሚፈቅድላቸው ውጪ ለሶስተኛ ዙር በምርጫ ለመወዳደር መወሰናቸውን ተከትሎ በአገሪቱ የተቀሰቀሰው ግጭት በዚህ ሳምንትም ያገረሸበት ሲሆን  የአገሪቱ የፓርላማና ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለሶስተኛ ጊዜ ዳግም መራዘሙን ቢቢሲ ዘገበ፡፡ በአገሪቱ ያለው ሁኔታ ሰላማዊ ምርጫን ለማከናወን አያስችልም በሚል ምርጫውን እንዲያራዝሙ ከአፍሪካውያንና ምእራባውያን መንግስታት ጫና ሲደረግባቸው የቆዩት ፕሬዚዳንቱ፣ ምርጫው እንዲራዘምና በመጪው ነሃሴ ወር መጨረሻ እንዲካሄድ መወሰናቸውን ከትናንት በስቲያ አስታውቀዋል፡፡
ከአገሪቱ ዋነኛ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች አንዱ የሆኑት አጋቶን ሩዋሳ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፣ ፕሬዚዳንት ንኩሩንዚዛ አምባገነን መሪ ስለሆኑ ከስልጣናቸው መውረድ አለባቸው ያሉ ሲሆን፣ የጸጥታ ሁኔታው ሳይሻሻል፣ ገለልተኛ የምርጫ ኮሚሽን ሳይመረጥና የግል ሚዲያው ላይ የሚደረገው ጫና ሳያበቃ በአገሪቱ ምርጫ ሊከናወን አይችልም ብለዋል፡፡ የብሩንዲ ምርጫ ከዚህ ቀደም እንዲራዘም በተወሰነው መሰረት፣ የፓርላማ ምርጫው ትናንት፣ የፕሬዚዳንታዊ ምርጫው ደግሞ በሰኔ ወር መጨረሻ ሊካሄድ ቀን ተቆርጦ ነበር፡፡
ፕሬዚዳንቱ በምርጫ ለመወዳደር መወሰናቸውን ማስታወቃቸውን ተከትሎ ያልተሳካ መፈንቅለ መንግስት መካሄዱና በአገሪቱ በተቀሰቀሰው ግጭት ከ20 በላይ ዜጎች መሞታቸውን፣ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ብሩንዲያውያንም ወደ ጎረቤት አገራት መሰደዳቸውን ባለፈው ሳምንት መዘገባችን ይታወሳል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

  ከአለማችን ታላላቅ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች አምራች ኩባንያዎች ተርታ የሚሰለፈው የጃፓኑ ሻርፕ ኩባንያ፣ በያዝነው የፈረንጆች አመት  ብቻ 1.45 ቢሊዮን ዶላር ይከስራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ሮይተርስ ዘገበ፡፡
ከቅርብ አመታት ወዲህ እየደረሰበት ካለው ኪሳራ ለማገገም ደፋ ቀና ማለቱን የቀጠለው ሻርፕ፣ በዘንድሮው አመት  1.45 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ ይደርስበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጃፓኑ ኮዮዶ ኒውስ ይፋ ያደረገውን መረጃ ጠቅሶ ዘገባው ገልጧል፡፡
ኩባንያው ባለፈው አመት 222 ቢሊዮን የጃፓን የን መክሰሩን ያስታወሰው ዘገባው፣ የአምናው ኪሳራው ባለፉት አራት አመታት ከደረሱበት ኪሳራዎች በሶስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝም ገልጧል፡፡ ኩባንያው ባለፉት አመታት ለከፍተኛ ኪሳራ የተዳረገው በተለያዩ አለማቀፋዊና ውስጣዊ ምክንያቶች መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፣ ከእነዚህም መካከል የምርቶች ሽያጩ መቀነሱ፣ የገበያ ውድድሩ ከፍተኛ መሆኑና የወጪዎች መብዛት ይጠቀሳሉ ብሏል፡፡ ሻርፕ ባለፈው አመት በአለም ዙሪያ ከሚገኙ 49 ሺህ ሰራተኞቹ መካከል 10 በመቶውን ከስራ እንደቀነሰና ከእነዚህም መካከል 3ሺህ 500 የሚሆኑት በጃፓን ይሰሩ የነበሩ መሆናቸውንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ
Page 12 of 16