እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ልጀቷ አባቷን…“አባዬ ማንን ላግባ፣ መልከ መልካሙን አበበን ወይስ ታማኙን ከበደን?” ትለዋለች፡ አባትም…
“ከበደን አግቢው፣” ይላታል፡፡
“ለምን?” ስትለው ምን ቢል ጥሩ ነው…
“ላለፉት ሰባት ወራት በመጣ ቁጥር ገንዘብ ስበደረው ቆይቻለሁ፡፡ ግን ይህ ሆኖ በሳምንት ሁለት ጊዜ አንቺ ዘንድ መምጣቱን አላቋረጠም፡፡”
ልጄ¸..ኑሮ ሲከፋ አባትም የልጁን ትዳር ጓኛ ከራሱ ‘ናሽናል ኢንተረስት’ (ቂ…ቂ…ቂ…) ማየት ቢጀምር ምን ይገርማል!
ነገርዬው… “እንደምንም ብሎ ይሄስ ቀን ባለፈ!” ሆኗላ!
ስሙኛማ… የምር ግን ኑሮ ከባድ፣ በጣም ከባድ እየሆነ ነው፡፡ አብዛኛውን ህዝብ ጧት ማታ ስለ ኑሮ የሚያማርረው ‘አልቃሻ’ ስለሆነ ወይም ‘ወተት ሲያቀርቡለት ፋንዲያ የሚል’ ስለሆነ አይደለም፡፡ ወይም “እነ እከሌ አማረባቸው፣ አለጠለጡ!” ብሎ ‘ስለሚመቀኝ’ አይደለም፡፡ ግራ ስለገባው ነው። ከቤቱ ሲወጣ መሳቀቅ፣ እቤቱ ሲመለስ ይበልጥ መሳቀቅ ስለበዛበት ነው፡፡ በየእምነታችን ስፍራ እየሄድን ተደፍተን… “እንደምንም ብሎ ይሄስ ቀን ባለፈ!” የምንለው…ችጋር ጠሪ ስለሆንን አይደለም፡፡
የምር እኮ የመሠረታዊ ዕቃዎች ዋጋ በየሁለትና ሦስት ቀኑ ሲያሻቅብ ‘ሀይ’ የሚል አለመኖሩ… አለ አይደል… “እረኛ የሌለን መንጋ…” መሆናችን ያሳዝናል፡፡ እናማ…“እንደው መጨረሻችን ምን ይሆን የምንለው ወደን ሳይሆን የምንለው ሲጠፋን ነው፡፡
“እንደምንም ብሎ ይሄስ ቀን ባለፈ!” የምነለው ቢቸግረን ነው፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል……ኑሮን በተመለከተ ዛሬ የኤፍ.ኤም. ጋዜጠኛ መሆን አምሮኛል፡፡
የኑሮን ነገር በተመለከተ ዛሬ ቃለ መጠይቅ ልናደርግ ስቱዲዮአችን አንድ እንግዳ አሉ፡፡ ወ/ሮ እንደልቧ አገሬ ሲሆኑ የቤት እመቤትና የአምስት ልጆች እናት ናቸው፡፡ አድማጫቾቸን በቀጥታ የስልክ መስመር ወይም በጽሁፍ መልእክተ ሀሳባቸሁብን ግለጡልን፡፡
ስምዎን ቢነገሩኝ፡፡
(ይሄኔ በልቧ “ማማሲያዬን ይዤ በመጣሁ ኖሮ፣ አናቱን የቻይና ብርጭቆ አደርገው ነበር!” ሳትል አትቀርም፡፡)
“እንደልቧ አገሬ እባላለሁ፡፡”
“ኑሮን እንዴት ይዘውታል?”
“ምን አልከኝ?”
“ኑሮን እንዴት ይዘውታል?”
“እንዴት ይዘውታል ብሎ ነገር ምንድነው! ኑሮ ጉሮሯችን አንቆ ትንፋሽ አሳጥቶን እንዴት ይዘውታል ትለኛለህ!”
“ይቅርታ…ኑሮ እንዴት ይዞዎታል?”
“እንዴት የያዘኝ ይመስለሀል…በርበሬ ኪሎ መቶ ሠላሳ ብር ገብቶ፣ ቅቤ ሁለት መቶ ሰባ ብር ገብቶ…ሦስት ራስ ሽንኩርት ዋጋው ራስ ላይ ወጥቶ እንዴት ይዞሻል ትለኛለህ!”
(“እንደምንም ብሎ ይሄስ ቀን ባለፈ!” የሚያሰኙ ነገሮች ብዙ ናቸው፡፡)
“ማለት የፈለግሁት…ይቅርታ አድማጭ መስመር ላይ አለ…ሀሎ አድማጫችን!
“ሀሎ! ‘ወይ ኑሮ፣ ወይ ኑሮ’ ፕሮግራም ነው?”
“ነው፡፡”
“አስተያየት ለመስጠት ነበር…”
“እሺ ማን እንበል ከየት ነው?”
“ቹቹ ነኝ፣ ከሀያ ሁለት…ምን ለማለት ፈልጌ ነው፣፣ ሴትዮዋ አምስት ልጅ ወልደው እሰካሁን በኑሮ ክፋት ገዳም አለመግባታቸው አድናቂያቸው እንደሆንኩ ለመግለጽ ነው፡፡”
“እርሶስ ኑሮ እንዴት ነው ይላሉ...”
“እነሱ ምን ቸገራቸው፣ ገበያ አይወጡ መርካቶና አትክልት ተራ የት እንዳለስ ያውቁታል?  ውስኪያቸውን እያንቃረሩ…“ ቀጭ!
(“እንደምንም ብሎ ይሄስ ቀን ባለፈ!” የሚያሰኙ ነገሮች ብዙ ናቸው፡፡)
“ይቅርታ ስልኩ ተቋርጧል…ወ/ሮ እንደልቧ…አሁን ያለውን የኑሮ ጫና ለመቀነስ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?”
“እና ምን አውቃለሁ…ነጋዴውን አንድ ይበሉልና! መንግሥት ስንበዘበዝ ዝም ብሎ የሚያየው ለምንድነው?”
“ቴክኒሻኗ አድማጭ ገብቷል እያለችኝ ነው…ሀሎ!”
“ሀሎ፣ ማን እንበል?”
“ቲቲ ነኝ ከአዲስ አበባ…”
“እሺ ቲቲ ሀሰብዎ ምንድነው?”
“ኸረ አንቱ አይደለሁም!”
“ተማሪ ነሽ ቲቲ?”
“አዎ…ግን ለምንድነው ኬክ ቤቶች አንድ የማይሏቸው! አንድ ፎርስት ኬክ ሠላሳ ብር እየሸጡ…እማዬ ትሙት ሲያስጠሉ!”
“እሺ ቲቲ መልእክትሽን አስተላልፈናል፡፡”
(እነ ቲቲ ዘንድም “እንደምንም ብሎ ይሄስ ቀን ባለፈ!” የሚያሰኙ ነገሮች ብዙ ናቸው፡፡)
“ደዋያችን ስለሰጠሽው ሀሳብ እናመሰግናለን… ወ/ሮ እንደልቧ በአሁኑ ጊዜ አምስት ልጆች ማስተዳደር አስቸጋሪ አይሆንም?”
“ተው እባክህ… እንኳን ለእነሱ ለዘመድ እንተርፍ ነበር…ክፉ ዘመን መጣና…”
“ይቅርታ አድማጭ ገብቷል…ሀሎ አድማጫችን ማን እንበል?”
“ስሜ ይቆይልኝ፡፡”
“እሺ ስለ ኑሮ ያለዎትን ሀሳብ ቢያካፍሉን፡፡”
“መጀመሪያ ነገር ለማሰብ መብላት ያስፈልጋል፣ ምኑን በልተን እናስብ! አገሩ ሁሉ ወሮበላ…”
“ይቅርታ አድማጫችን ከርእሳችን ባይወጡ…”
“አልኩህ እኮ… በየቦታው ያለው ሌባ ብቻ ነው…”
“አሁን እየተነጋገርን ያለነው ስለ ኑሮ ነው፡ አጠቃለይ ሃሳብዎን ቢገልጹልን፡፡”
“እኔም እኮ ስለ ኑሮ ነው የማወራው፣ ስማ ቀበሌያችን እንደ ቀንድና ጭራ የሌለው የሸማቾች…” ቀጭ!
(“እንደምንም ብሎ ይሄስ ቀን ባለፈ!” የሚያሰኙ ነገሮች ብዙ ናቸው፡፡)
“ይቅርታ ስልኩ ተቋርጧል፡፡ ከቻልን ደዋያችንን ደግመን ልናገኛቸው እነሞከራለን፡፡” (“እሱን እንኳን ተወው!” በሉኛ፡፡)
እናማ የዕለት ከዕለት ኑሯችንን በተመለከተ… “እንደምንም ብሎ ይሄስ ቀን ባለፈ!” የሚያሰኙን ነገሮች መአት ናቸው፡፡
ሦስትና አራት ብር ሲጨመር… አለ አይደል… “ቁ!…ቁ!…” (“እሪ!” እንደማለት) ልንል ምንም አይቀረን ነበር፡፡ አሁን ግን አምጥተው ‘ሲዘረግፉብን’ ዝም ብለን እያያን ነው፡ የእኛ ትከሻ ለመልመድ ማን ብሎት! በርበሬ በአጭር ወራት ወደ ሁለት መቶ ከመቶ ሲያድግ “ቁ!…ቁ!…” ማለት አቅቶናል፡፡
ስሙኝማ… ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ይቺን ስሙኝማ…ሴትዮዋ ሱፐርማርኬት ውስጥ እያንጎራጎረችና እየዘፈነች ነበር፡፡
“ዛሬ በጣም ደስ ብሎሻል፡፡ ምን ተገኘ?”
“አዎ…ትልቅ ቤት አለኝ፣ ሁለት ቆንጆ ልጆች አሉኝ፡ ባንክ ገንዘብ አለኝ፣ የባሌ የህይወት ኢንሹራንስ መቶ ሺህ ዶላር ነው…እሱ ደግሞ ጤናው ተቃውሶ አንድ ሐሙስ ነው የቀረው፡፡”
ሱፐርማርኬት ውስጥ የምታንጎራጉር ሴት ከገጠመቻችሁ ወይ ‘ሲንግል’ ለመልቀቅ እየተዘጋጀች ነው፣ ወይ የህይወት ኢንሹራንስ የገባው ባሏ ታሞ አልጋ ላይ ነው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
እናላችሁ…የዕለት በዕለት ኑሯችንን በተመለከተ… አለ አይደል… “እንደምንም ብሎ ይሄስ ቀን ባለፈ!” የሚያሰኙ ነገሮች በላይ በላይ እየተከመሩብን ነው፡
ጫንቃችን ነጻ የሚሆንበትን ዘመን ያቅርብልንማ!
ደሀና ሰንብቱልኝማ!

Published in ባህል

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ በአለቃው የተመረረ ቻይናዊ፣ ቢሮ ይገባና ለአለቃው እንዲህ ይላቸዋል፡-
“ከእንግዲህ እንደ በረዶ ዳክዬ ወደሩቅ አገር መሄድ ይሻላል”
አለቅዬውም፤
“ምን ለማለት ፈልገህ ነው?” ይሉታል፡፡
ቻይናዊው እንዲህ ሲል መለሰ፣
“አውራ ዶሮን ልብ ብለው ተመልክተዋል? የአምስት ምግባረ ሰናይ ተምሳሌት ነው፡-
ጭንቅላቱ ላይ ያለው ጉትያ የጥሩ ዜግነት ምልክት ነው፡፡
የእግር ጥፍሮቹ የኃይለኛነትና የጥንካሬ ምልክት ናቸው፡፡
ማንኛውንም ጠላት ለመጋፈጥ ያለው ቁርጠኝነት የድፍረት ምልክት ነው፡፡ ምግብ ባገኘ ሰዓት ለሌሎች ለማካፈል መቻሉ የደግነትና የቸርነት ምልክት ነው፡፡
በመጨረሻም በየሌሊቱ ሰዓቱን አክብሮ የሚጮህልን ደግሞ የዕውነተኝነት ተምሳሌት ነው፡፡
እነዚህን የመሰሉ አምስት ተምሳሌትነት ያለውን ዶሮ፣ እኛ የገበታ ሳህናችንን ለመሙላት ስንል በየቀኑ እናርደዋለን፡፡ ይሄ ለምን ይመስልዎታል? ከእዚሁ ቅርብ፣ አጠገባችን ስለምናገኘው ነው፡፡ በሌላ በኩል የበረዶ ዳክዬ በሺ ኪሎ ሜትር የሚቆጠር ርቀት ውቂያኖስ አቋርጣ ትበርራለች፡፡ ሲሻት በየአትክልቱ ማህል ታርፋለች፡፡ ሲሻትም በየወንዙ ዳር አሣ ታድናለች፡፡ ቢሻት ደግሞ ትናንሽ የውሃ ዔሊ ትመገባለች፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ የእርሻ ማሽላ ትበላለች፡፡ እንደ አውራ ዶሮ አምስት ምግባረ ሰናይ ባይኖራትም ትልቅ ዋጋ እንዳላት አድርገን እናደንቃታለን። ለምን? በእጃችን ስለሌለች! ይሄ ስለሆነ እኔም የበረዶ ዳክዬ ሆኜ መብረርን መረጥኩ”
*             *            *
“በእጅ ያለ ወርቅ እንደ መዳብ ይቆጠራል” እንደማለት ነው፡፡ በቅርባችን እጃችን ውስጥ ያለን ሀብት እንዴት እንደምንገለገልበት አለማወቅ ብቻ ሳይሆን አጎሳቁለንና ከአግባቡ ውጪ ስለምናዛባው ለድህነት ራሳችንን እናጋልጣለን፡፡ የበላይ ኃላፊዎች የበታች ሰራተኞችን ማጉላላትን የሥልጣን ማሳያ ካደረጉት መልካም አስተዳደር ስም ብቻ ሆኖ ይቀራል፡፡ በእጃችን ያለውን የሰው ኃይል ማባከንን የሚያህል የድህነት መነሾ የለም፡፡ ከአያያዝ ይቀደዳል ነው፡፡ ጉዳቱ እያደር የሚታወቀው፤ የመልካም አስተዳደር መጥፋት፣ ባለብን ድህነት ላይ ሲደረብ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነው፡፡ በየውስጣችን አገርን የማሰብ ጥንካሬ ከሌለ፣ ላይ ላዩን ብቻ ማውራት እስክንጋለጥ ብቻ ነው የሚያበላን፡፡
ሾፐንአወር፤ “አዕምሮ ወደ ውስጥ አስቦ የመጠንከር ጉዳይ እንጂ ወደ ውጪ የመስፋፋት ጉዳይ አይደለም” ይለናል፡፡ አንጎል የተሰጠን ውስጣችንን እንድናጠናክርበት ነው ማለት ነው፡፡
በአካባቢያችን ያለውን አዕምሮ በቅጡ ካልተገለገልንበት ኑሮ ውሃ ወቀጣ ይሆናል፡፡ ራዕይ ይሟጠጣል፡፡ ምሁሮቻችንን አናርቃቸው፡፡ አንግፋቸው። ይልቁንም በአግባቡ እንጠቀምባቸው፡፡ የሚቆጨን፤ ጊዜው ካለፈና አዋቂዎች ከራቁ በኋላ ነው፡፡ ላሮቼፎኮ የተባለ ፀሐፊ፤
“በቅርብ አለመገኘት ትናንሽ መውደዶችን የባሰ ያሳንሳቸዋል፡፡ ትላልቆቹን ግን ያቀጣጥላቸዋል፡፡ ልክ ንፋስ ሻማን እንደሚያጠፋውና ትላልቅ ቃጠሎን ግን እንደሚያራግበው፡፡” ይለናል፡፡ በተቻለ መጠን የመቻቻልን ዕሳቤ ማስፋት ተገቢ ነው፡፡ ሆደ ሰፊነት ከብዙ አባዜ ያድናል፡፡ ሩቅ ለመጓዝም ዋና መሳሪያ ነው። የፖለቲካችን ውሃ ልክ የመቻቻልንና የዲሞክራሲን ባህሪ በቅጡ ማወቅ ነው፡፡ ይህ ዕውቀት ነው፤ ከተንኮል፣ ከበቀልና ከማናለብኝ አካሄድ የሚገላግለን፡፡ “ቆይ ነገ ባልሰራለት!” ዓይነት አስተሳሰብ፤ ከየትኛውም ወገን ቢመጣ ደግ አስተሳሰብ አይደለም፡፡
ስትራቴጂያችንን የሰመረ የሚያደርገው በወቅቱ ስንጀምረው ነው፡፡ በቅንነት፣ በጠዋት ካልተንቀሳቀስን ማታ መቸገራችን አይቀሬ ነው፡፡
“…. ያለንን ኃይል/አቅም አሰባስበን በአትኩሮት ወደሥራ እንደመግባት ኃያል ስትራቴጂ የለም” ይለናል፤ ካርል ፎን ክላውስዊዝ፡፡ በተለይ በምርጫ ማግሥት እንዲህ ማሰብ መልካም ነው፡፡ በሁሉም ወገን ያለው ችግር በራስ አለመቆም ነው። መደጋገፍ ትልቅ ፋይዳ ያለው ይሁን እንጂ ሁሌ ደግፉኝ ግብ አይደለም፡፡ ሁሌ ተሸከሙኝም ጤና አይሆንም፡፡ የሚመረጠው በራስ መተማመን፣ በተግባር ራስን ማወቅና በራስ መቆም ነው፡፡ አለበለዚያ “አንገቷን ደግፈው ቢያስጨፍሯት ያለች መሰላት” የሚለው ተረት ዕውን ይሆናል፡፡  

Published in ርዕሰ አንቀፅ

 ከህወሓት ጋር ትግል የጀመሩ ብቸኛው የአማራ ተወላጅ ነበሩ
በ40ኛው የህወሓት በዓል ላይ ስማቸው አልተወሳም - ቤተሰቦች
አቶ አብጠው ታከለ ማናቸው? ከህወሓት  ጋር በምን ተገናኙ?

      ከህወሓት መስራቾች አንዱ እንደሆኑ የሚነገርላቸው የአማራ ተወላጁ አቶ አብጠው ታከለ (በበረሃ ስማቸው ሚካኤለ)፤ የትግል ታሪክ ተድበስብሶ መቅረቱን የሚናገሩት ቤተሰቦቻቸው፤ በጉባኤዎችም ሆነ በምስረታ በዓላት ላይ የእኚህን ታጋይ ስም የሚያነሳ አካል መጥፋቱ እንዳሳዘናቸው ለአዲስ አድማስ ገለጹ፡፡  
አቶ አብጠው የዛሬ 40 አመት ህወሓትን ከመሠረቱት 10 ታጋዮች አንዱ እንደሆኑ የህወሓት ጽ/ቤት አረጋግጧል የሚሉት ቤተሰቦች፤ እስካሁን ግን ይፋዊ የታሪክ እውቅና አልተሰጣቸውም ሲሉ ቅሬታቸውን ሰንዝረዋል፡፡ “ኢህአዴግ ሥልጣን ከያዘ በኋላ በተካሄደ የትኛውም የህወሓት ጉባኤ ላይ አባታችን የተሣትፎ ግብዣ እንኳ ቀርቦለት አያውቅም” ያሉት የአቶ አብጠው ልጅ አቶ ካሣሁን አብጠው፤ አባታችን ካለፈ በኋላም ታሪክና ገድሉን ትውልድ እንዲያውቀው በሚያስችል መልኩ አለመነገሩ ቅር አሰኝቶናል” ይላሉ፡፡
ህወሐት 40ኛ ዓመት የልደት በአሉን ባከበረበት ወቅትም ሆነ ብአዴን 35ኛ ዓመት የምስረታ በአሉን ሲያከብር፣ ከትግሉ ጠንሳሾች አንዱ የነበሩት ታጋይ ሳይታወሱ መቅረታቸውን ልጃቸው ይናገራሉ፡፡ ይሄንኑ ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንዲሁም ለህወሓትና ብአዴን ከፍተኛ አመራሮች ለማስታወስ ልጃቸው አቶ ካሣሁን አብጠውና ባለቤታቸው ወ/ሮ አለም አፅብሃ ሰሞኑን ከሠሜን ጐንደር አዲስ አበባ ድረስ  ቢመጡም፣ የሚያነጋግራቸው አጥተው መመለሳቸውን ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡
ታጋይ አብጠው (ሚካኤለ)፤የህወሓት መስራች ከነበሩት 10 ግለሰቦች አንዱ መሆናቸውን የህወሓት ጽ/ቤት ማረጋገጡን ሚያዝያ 21 ቀን 2007 ዓ.ም ለብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽ/ቤት በፃፈው ደብዳቤ ያስታወቀ ሲሆን ታጋዩ ለትግሉ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ተገቢውን የታሪክ ቦታ እንዲያገኝ አስገንዝቦ፣ ለቤተሰቦቻቸውም ህወሓት አቅሙ በፈቀደ መጠን ክትትልና እንክብካቤ እንደሚያደርግ ገልጾ ነበር ይላሉ፡፡ “ግለሰቡ ደደቢት ከደረሱ 10 የህወሓት መስራቾች አንዱ ናቸው” ሲል ህውሓት በደብዳቤው ላይ ጠቁሟል፡፡  
“ሆኖም ለቤተሰቡ ቃል የተገባው እንክብካቤም ሆነ ለአባታችን ይሰጣል የተባለው ተገቢ የታሪክ ቦታና ይፋዊ እውቅና የውሃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል፤ ይህን ለማስታወስ አዲስ አበባ ድረስ ብንመጣም በሩን ከፍቶ የሚያነጋግረን አካል አጣን” ብለዋል ቤተሰቦቻቸው፡፡
አቶ አብጠው አሁን ለተገኘው ሠላም፣ ልማትና ዲሞክራሲ ጉልህ አሻራ ያስቀመጠ ታጋይ በመሆኑ ህወኃት ለእዚህ ታጋይ ከደብዳቤ ያለፈ ይፋ እውቅና እንዲሰጠው አበክረን እንጠይቃለን ብለዋል፡፡ ቤተሰቦቻቸው በአብዛኛው በግብርና የሚተዳደሩ እንደሆኑ በመጠቆምም እስካሁን ግን ለታጋይ ቤተሰቦች የሚደረገው ድጋፍና እንክብካቤ ጨርሶ ተደርጐላቸው እንደማያውቅ ገልጸዋል፡፡  
 አቶ አብጠው ታከለ ማን ናቸው?
ታጋይ አብጠው ታከለ፤ ከእናታቸው ከእማሆይ ወለተ ስላሴ፣ ከአባታቸው አቶ ታከለ አመራ በሰሜን ጐንደር፣ አዲአርቃይ ወረዳ፣ ዛሬማ የምትባል ከተማ ተወለዱ፡፡ በወጣትነታቸው በግብርና እና በንግድ ስራ ላይ ሳሉ ነው ወ/ሮ አለም አፅብሃን ያገቡት፡፡ በዚህም ሳቢያ ለወ/ሮ አለም የስጋ ዘመድ ከነበሩት የህወሓት ዋነኛ መስራቾች ገሠሠ አየለ (ስሁል) እና ብርሃኔ አየለ ጋር የጋብቻ ዝምድና ተፈጠረ፡፡
 በ1965 እና 66 አካባቢ የትጥቅ ትግል ለማካሄድ እነ ገሠሠ አየለ ሲመክሩ፣ አቶ አብጠው አገር የመሰከረላቸው በረሃ አዋቂና ጀግና እንደነበሩ ያውቁ ነበር የሚሉት ልጃቸው፤ የካቲት 8 ቀን 1967 ዓ.ም እነ ገሠሠ አየለ (ስሁል) ደርግን ለመደምሰስ ያለው አማራጭ የትጥቅ ትግል መሆኑን ሲወስኑ ወደ አቶ አብጠው ዘንድ የትግል ጥሪ ያደርሳሉ፡፡ እሳቸውም ጥሪውን ወዲያው ተቀብለው፣ ያፈሩትን ንብረት ሜዳ ላይ በትነው፣ የወላጅ አባታቸውን የ40 ቀን ተዝካር እንኳ ሳያወጡ በቀጥታ ጉዞ ወደ ሽሬ ሆነ፡፡ ሽሬ ላይ ከአቶ ገሠሠ ጋር ስለ ትግሉ ጥንስስ ተወያዩ። እስከ የካቲት 10 ቀን 1967 ድረስም በጉዳዩ ላይ ሲመክሩ ቆዩ፡፡ የካቲት 11 ለትግል ወደ ደደቢት በረሃ ተጓዙ፡፡
በ1999 ዓ.ም ከትግሉ ጠንሳሾች አንዱ ለነበሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ስዩም መስፍን በፃፉት ደብዳቤ ላይም ለትግሉ ያበረከቱትን አስተዋፅኦ በዝርዝር በመግለፅ ሊያስታውሷቸው ሞክረዋል። እንዴት በረሃን መቋቋም እንደሚቻል ምክርና ማበረታቻ፣ በረሃ ላይ ቂጣ እንዴት ድንጋይ ላይ እንደሚጋገር፣  ወፍን ተከትሎ በመጓዝ የጫካ ማር እንዴት መብላት እንደሚቻል፣ አደን እንዴት እንደሚታደን ለትግል ጠንሳሾቹ ሥልጠና መስጠታቸውን በደብዳቤያቸው ያስታወሱት አቶ አብጠው፤ የትግል ጓደኞቻቸው በረሃብ ምክንያት በህይወትና ሞት መካከል በነበሩ ጊዜ የዱር እንስሳት እያደኑ ይመግቧቸው እንደነበር ያወሳሉ፡፡ በትግሉ ወቅት ለበራሪ ወረቀት ማባዣ ማሽን አስመጥተውም ለአገልግሎት እንዲውል ማድረጋቸውንም ይጠቅሣሉ፡፡
ሰኔ 10 ቀን 1967 ዓ.ም አቶ ገሠሠ አየለ፤ የአቶ አብጠውን ባለቤት ደርግ እንዳይገድልባቸው ሄደው ቦታ እንዲያስይዟቸው በነገሯቸው መሰረት፣ የደርግን ክትትልና ጫና ተቋቁመው፣ከባለቤታቸው ጋር ለመገናኘት ችለዋል፡፡ በቀጠሉት የትግል ዓመታትም፣ በደባርቅና በአካባቢው ያለውን የደርግ እንቅስቃሴ እያጠኑ ደደቢት ላሉት ታጋዮች መረጃ ያቀብሉ እንደነበር የሚናገሩት ቤተሰቦቻቸው፤ በስለላና በመረጃ ስራ ላይ ሳሉ በአንድ አውደ ውጊያ ላይ አንድ አይናቸውን እንዳጡም ይገልጻሉ፡፡ ከቁስላቸው ካገገሙ በኋላ በ1978 ዓ.ም ከህወሓት መስራች አንዱ የሆኑት አቶ አስገደ ገ/ሥላሴ፣ የዛሬማን ህዝብ ሰብስበው፤“አሁን ላለንበት ደረጃ ያደረሰን አቶ አብጠው ነው” በማለት የህወሓት መስራችነታቸውን ከመሰከሩላቸው በኋላ አንድ ክላሽ መሸለማቸውን ቤተሰባቸው ያስታውሳል፡፡  
አቶ አብጠው ከትግል በኋላም በአካባቢያቸው ከፀረ-ሠላም ኃይሎች ጋር ሲዋጉ እድሜያቸውን እንዳሳለፉ የሚገልፁት ቤተሰቦቻቸው፤“አባታችን ባይማርም ለሰው ልጅ ሰብአዊ መብቶች መከበር አጥብቆ የሚቆረቆር ሰው ስለነበር፣ በማህበረሰቡ ዘንድ አንቱታንና ከበሬታን ተጎናጽፏል፤በትግል አጋሮቹ መዘንጋቱና ስሙን እንኳ የሚጠቅስ አካል መጥፋቱ ግን በእጅጉ አሳዝኖናል” ሲሉ ቅሬታቸውን ገልፀዋል፡፡
ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ በኋላ በ1993 ዓ.ም ለህክምና ወደ አዲስ አበባ መጥተው፣ በአቶ ስዩም መስፍን አማካኝነት ጦር ኃይሎች ሆስፒታል ለ3 ወራት ተኝተው ከታከሙ በኋላ “አንተ ወታደር አይደለህም” ተብለው ከሆስፒታል እንዲወጡ በመደረጋቸው፣ ወደ ትውልድ ቀዬአቸው መመለሳቸውን ልጃቸው ያስታውሳሉ፡፡ ከዚያ በኋላም ቢሆን ወደ አዲስ አበባና መቀሌ በመመላለስ፣ የታጋይነታቸውና የህወሓት መስራችነታቸው ጉዳይ እውቅና አግኝቶ፣ እንደ ማንኛውም ታጋይ ድጋፍና እንክብካቤ እንዲደረግላቸው በተደጋጋሚ ከመጠየቅ ወደ ኋላ ባይሉም ሰሚ ጆሮ አለማግኘታቸውን ቤተሰቦቻቸው ያስረዳሉ፡፡
በ1999 ዓ.ም በከፍተኛ የአንጀት ህመም መሰቃየታቸውንና ተገቢውን ህክምና ሊያገኙ ባለመቻላቸው ወደ ዋልድባ ገዳም ገብተው የመነኮሱ ሲሆን ከአንድ አመት በኋላም ህይወታቸው ማለፉን ልጃቸው ገልጸዋል፡፡  በህወሓት በኩል ለአንድ ጀግና ታጋይ የሚደረገው ክብር ሁሉ ቢነፈጋቸውም ከ1ሺህ በላይ የሚሆን የአካባቢው ህዝብ በራሱ ተነሳሽነት፣ በክብር ባንዲራ ወጥቶላቸው፣ በታላቅ ሥነ ሥርዓት በመነኮሱበት የዋልድባ ገዳም እንደቀበሯቸው ቤተሰቦቻቸው ይናገራሉ፡፡           
የህወሓት አንጋፋ ታጋይና አመራር የነበሩት አቶ ገብሩ አስራት ስለታጋይ አብጠው ተጠይቀው፤ግለሰቡን በአካል ባያውቋቸውም ከህወሓት መስራቾች አንዱ መሆናቸውን እንደሚያውቁ ገልፀው፣ከህወሓት ጠንሳሽ አቶ ገሠሠ አየለ (ስሁል) ጋርም ዝምድና እንዳላቸው አውቃለሁ ብለዋል፡፡
 ህወሓት ታሪክ ለሰሩ የቀደሙ ታጋዮች ተገቢውን ክብር የማይሰጠው፣ ግለሰቦችን እንደ አገልግሎት እቃ ብቻ ስለሚመለከት ነው የሚሉት አቶ ገብሩ፤ አንድ ሰው ከእነሱ በሃሳብ ከተለየ ያበረከተው አስተዋፅኦ ሁሉ ገደል ይገባና በጠላትነት ይፈረጃል ይላሉ፡፡ የግለሰቡን ታሪካዊ ገድልም ለማስታወስ አይሹም ብለዋል- አንጋፋው የህወሓት ታጋይ አቶ ገብሩ፡፡ “እኔም ሆንኩ የሃሳብ ልዩነት ፈጥረን ከህወሓት የወጣን ሰዎች፣ እስከ ትግሉ ፍፃሜ ድረስም ሆነ ከዚያ በኋላ ለኢትዮጵያ ህዝብ ብዙ ታግለናል” ያሉት አቶ ገብሩ፤ ከህወሓት በሃሳብ ስንለይ ግን በአንድ ድምፅ እንደ ጠላትና ከሃዲ ተደርገን ነው የተፈረጅነው፡፡ ምናልባት አቶ አብጠው (ሚካኤል) ጉዳይም ተመሳሳይ ሊሆን ይችላል፤ ሲሉ ግምታቸውን ተናግረዋል፡፡                        
ነሐሴ 1 ቀን 2002 ዓ.ም በወጣው የአዲስ አድማስ ዕትም፣ “ከህወሓት መስራቾች አንዱ በመነኮሱበት ገዳም አረፉ” በሚል ርዕስ የታጋይ አብጠው ታከለን ዜና ዕረፍት መዘገባችን  ይታወሳል፡፡                 

አረንጓዴ! ቢጫ! ቀይ!...እነዚህ ሦስት ቀለማት እንደ ጉልቻ ለሦስት ተጣምረው ሀገራችንን የሚገልፁና ማንነታችንን የሚያሳዩ ህያዋን ናቸው፡፡ ቁጥራቸው እንደ ስላሴዎች ሦስት፣ ቀለማቱ እንደ ፀሐይ አብሪና እንደ ጨረቃ ደማቅ ናቸው፡፡
አረንጓዴው ልምላሜን ያሳያል፡፡ ቢጫው ተስፋችንን ሲገልፅ፤ ቀዩ በደም የፀናንና የገነን መሆናችንን ያመለክታል፡፡ ኢትዮጵያችን በሦስቱ ቀለማት ጥምረትና ውህደት ትመሰላለች፡፡ ቀለማቱ በአባቶቻችን ጥረትና ድርጊት ህያው ሆነው የኖሩ፤ ወደፊትም የሚኖሩ ናቸው፡፡
አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ባንዲራችን የኩራታችን መገለጫ፣ የኩሩነታችን መታያ ናት፡፡ ይቺ ሰንደቅ ብዙ ደም ፈሶላታል፤ ብዙ ሰው ቆስሎላታል፤ ብዙ አጥንት ተከስክሶላታል፡፡
ዮፍታሔ ንጉሤ ለጀግኖች ሀገር ጠባቂ ኢትዮጵያውያን፤
“…ብዙ መናገር ሰው ያናንቃል፣
እውነት ከሆነ አንዱ ይበቃል፣
ያገሬማ ጀግና ቅልስልሱ
እንደ አንበሳ ሥጋ ነው ቀለቡ…” ሲሉ ስንኝ ቋጥረዋል፡፡
ይህቺ አገራችን ኢትዮጵያ የአባትና የእናቶቻችንን ስጋ በልታና ደማቸውን ጠጥታ፣ ቋሚ የሆነች ልዕልት ናት፡፡ ህያውነትዋም በመስዋዕትነት የተገኘ ነው፡፡ ባንዲራችን ተምሳሌት ናት፡፡ ኢትዮጵያ የተባለችው፣ የኛይቱ የትውልድና የዕድገት ምድር የሆነች ሀገር መታያ ትዕምርት! በባንዲራ የመሰልናት ወይም የምንመስላት ሀገራችን ችሮታዋ ብዙ ነው፡፡ የሀገራችንና የባንዲራችን ልዕልና ከዘመን ዘመን ሲሻገር ከእኛ ዘንድ ደርሷል፡፡ ቀደምት አባቶችና አርበኞች በቃል የማይገለጽ ግዙፍ መስዋዕትነት የከፈሉላት ምድር ናት፤ ኢትዮጵያ!
ዮፍታሔ ንጉሤ እንዲህ ይላሉ፡-
“…ሕይወቱን ጠብቆ የሞተ ላገሩ፣
በሕይወት ይኖራል ነፃነቱ ክብሩ፣
ደሜ ይፍሰስ የሚል ቢኖር ከድንበሩ፣
ሕይወትን ማጨድ ነው ደምን እየዘሩ፣
ሰፊ ነው ጫጉላ ነው ጠባብ መቃብሩ፣
ለሀገር መሞትን ማነው ሞት የሚለው፣
ለአገሩ ልጅ ሕይወት ለጠላቱ ሞት ነው፣…”
በሌላው “የሰንደቅ ዓላማ መዝሙር” የተባለ ግጥማቸው እንዲህ እያሉ ስንኝ ይደረድራሉ፡-
“ደሙን ያፈሰሰ ልቡ የነደደ፣
ባርበኝነት ታጥቆ ጠላት ያስወገደ፣
ንጉሡን አገሩን ክብሩን የወደደ
ነጻነቱን ይዞ መልካም ተራመደ፡፡
ገናናው ክብራችን ሰንደቅ ዓላማችን፣
ያኮራሻል አርበኝነታችን፡፡
ተጣማጅ አርበኛ በአገር መውደድ ቀንበር፣
ገዳይ ድል አድራጊ ደም አፍሳሽ ወታደር፣
አንቺን እያሰበ ይጓዛል ሲፎክር፣
ሰንደቅ ዓላማችን የነጻነት አገር…”
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ (ነፍሳቸውን ይማረውና) “ባንዲራ ጨርቅ ነው!” ቢሉም እኛ ግን “ባንዲራ ወርቅ ነው!” እንላለን፡፡ ይህን ብቻ ብለንም አናበቃም፤ “ባንዲራ ህይወታችን ነው!” ስንል እናክልበታለን፡፡ የህይወት መስዋዕትነት የተከፈለበት፤ እልፍ አዕላፎች የሞቱለት፤ እኛ ያሁኖቹ ወጣቶችም ስለ ክብሩና ታላቅነቱ፤ ስለ ህያውነቱና ዘላቂነቱ የምንታገልለት ነው፡፡
ባንዲራ ጨርቅ አይደለም፡፡ ባንዲራ ተራ ነገር አይደለም፡፡ ባንዲራችን በጥቂቶች ቢናቅና ቢንኳሰስም  ምንነቱ ከልባችን ውስጥ ሊወጣም ሆነ፤ በልባችን ውስጥ ሞቶ ሊቀበር አይችልም፡፡ እንደ ሀገራችን ሁሉ ባንዲራችንም ህልው ናት፡፡ ኢህአዴግ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ አቋሙን ቀልብሶ (ጨርቅ የተባለውን ባንዲራችንን አክብሮ ይሁን ወይም ኢትዮጵያውያን ለባንዲራቸው ያላቸውን ፍቅርና ክብር ተረድቶ ወይም ተቃዋሚዎችን አጀንዳ ለማሳጣት አስቦ እርግጡ ባይታወቅም የባንዲራ ቀን ብሎ ማክበር ጀምሯል) መልካም ነው፡፡
ሳይለወጡ እንደ የዕድሜ ባለፀጋ ድንጋይ፣ ለዘመናት ባህር ውስጥ ከመኖር፤ ውሎ አድሮም ቢሆን መለወጥ ቁም ነገር ነው፡፡ የኢህአዴግ የአቋም ለውጥ በመልካምነቱ የሚጠቀስና የሚወደስ ነው፡፡ የሚቀር ነገር ግን አለ፡፡ የባንዲራን ክብርና ታላቅነት እያወጁ፤ የሀገርን ታሪክ ደግሞ እየካዱ መኖር አይቻልም፡፡ መኖርማ ይቻላል፤ ነገር ግን ሁለቱ ነገሮች ፈጽሞ አብረው የሚሄዱና የሚታረቁ አይደሉም፡፡ ከባንዲራ ታሪክ የሀገር ታሪክ ይቀድማል፡፡ ሀገር ሳትኖር ባንዲራ አይኖርም፡፡ ሀገር በሌለበት ባንዲራ የለም፡፡ በባንዲራ ውስጥ ታምቆ የሚገኝ ታሪክ፣ የሀገር ታሪክ አንድ ገፅ ነው፡፡ ከታናሽ ታላቅ ይቀድማል፡፡ ሀገር ታላቅ ስትሆን ባንዲራ ታናሽ ናት፡፡ የባንዲራ ታናሽነት ባንዲራን የሚያሳንስና የሚያስንቅ ሳይሆን ፍቅርና እንክብካቤ የሚገባው መሆኑን የሚያስረዳ ነው፡፡
ባንዲራችን ሁሌም ሙሽራ ናት፡፡ ቬሎ ያልለበሰች ነገር ግን በውበት የደመቀች ሙሽራ! ጠዋት በክብር ተሰቅላ ማታ በክብር ትወርዳለች፡፡ ይህ አብዛኛውን ጊዜ የሚሆነው በትምህርት ቤቶች ነው፡፡ በመንግሥት መስሪያ ቤቶች አካባቢ ደግሞ ቀን ከሌት ስትውለበለብ ውላ ታድራለች፡፡ ዘወትር ስትርገበገብ ትኖራለች፡፡ እኛም በክብርና በፍቅር በተሞላ ልዩ ሁኔታ ቀና ብለን እያየናት ሀሴት እናደርጋለን፡፡
መንግሥታት ይመጣሉ፡፡
መንግሥታት ይሄዳሉ፡፡
ባንዲራ ግን ዘላለማዊ ናት!
ታሪክ እየመረመረ በሚጽፋቸው ተውኔቶቹ የሚታወቀው ፀሐፌ ተውኔት፣ አዘጋጅ፣ ተዋናይና ገጣሚ ጌትነት እንየው “ዘላለማዊ ነሽ” ብሎ በሰየመው ግጥሙ እንዲህ ይላል፤
“የቀስተ ደመና፣ የውበት አምሳያ
የትውልድ ጅረት፣ ዕድሜ መቀጠያ
የአብሮ መኖር ድባብ፣ ሕብር መጠለያ
የተበተነ ዘር፣ በአንድ መቋጠሪያ
መሆንሽን የረሱ
ማተብ የበጠሱ፣
የእምነትሽን ፅናት
የእውነትሽን ጥራት
በጊዜ መስታወት እያደር ያዩታል
ዘላለማዊነትሽን ዘላለም ያውቁታል፡፡…”
እነዚህ ከላይ የሰፈሩት ስንኞች ለቀድሞው የኢህአዴግ አቋም፣ መልስ---የተደረደሩ ይመስላሉ፡፡ ገጣሚው  እንዳለው፣ ኢትዮጵያዊያን ለባንዲራቸው ያላቸውን ፍቅርና ክብር ኢህአዴግ እያደር ሳይረዳው የቀረ አይመስልም፡፡ ያ ጥራዝ ነጠቅ አባባሉ ታርሞ፣ ሰንደቅ ዓላማችን ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ አድርጓል። ቀንም ሰይሞለታል፡፡ እኛም “ይሁን!” ብለን ከቃለ አጋኖ ጋር ተቀብለናል፡፡
ጌትነት እንየው ስለ ባንዲራ በጻፈው ግጥሙ እንዲህ ሲል ይቀጥላል፤
“የማንነቴ አርማ፣ ሰንደቅ ምልክቴ
የኢትዮጵያዊነት፣ ሞገስ በረከቴ
የሰውነት ክብሬ፣ የመንፈስ ፅናቴ
መነሻ መድረሻ፣ ስሬ መሰረቴ
መሆንሽን አውቄ
በአንቺ ስር ደምቄ
አንገቴን አቅንቼ
ሽቅብ ተመልክቼ
ስትውለበለቢ ካንቺ ያነበብኩት
ክብር ነው፣ ነፃነት፣ ፍቅር፣ እውነት፣ እምነት፡፡”
ባንዲራ ግዝፈት አላት፡፡ ግዝፈቷም ከትዕምርትነትዋ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ለዚችው ባንዲራችን ክብር ከጠላት ጋር ስንፋለም ኖረናል፡፡ ወደፊትም ስለ ባንዲራችን ከመጋደል ወደ ኋላ የምንል አይደለንም፡፡
በጌትነት የመጨረሻ ስንኞች ወጋችንን እንቋጭ፡-
“…አላማሽ ሰንደቁ፣ ስሩ የጠለቀ
ቀለምሽ ምስጢሩ፣ ቅኔው የመጠቀ
ፍቅርሽ መቋጠሪያው፣ ውሉ የጠበቀ
አይጥሉሽ - አይቆርጡሽ
አይክዱሽ - አይፍቁሽ፣
በሕይወት የዘሩሽ
በደም ያፀደቁሽ
አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ አርገው ያቆሙሽ
ሰንደቅ አላማዬ ዘላለማዊ ነሽ፡፡”

በሜኤሶ ደዋሌ የባቡር መስመር የእሳተ ጐሞራ ሥጋት አለ

   በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን እየተተገበሩ ያሉት የሃዲድ መስመር ዝርጋታዎች በውሉ መሰረት እየተከናወኑ መሆናቸውን ለማረጋገጥና የጥራት ደረጃቸውን ለመከታተል የሚያስፈልጉ ሰነዶችን ተቋራጮቹ ከቻይንኛ ወደ እንግሊዝኛ አስተርጉመው ለማቅረብ ባለመፈለጋቸው በሥራው ላይ እንቅፋት መፍጠሩ ተገለፀ፡፡ የፌደራል ዋናው ኦዲተር ባቀረበው ሪፖርት ላይ እንደተገለፀው፤ ሁሉም የባቡር ፕሮጀክቶች :-
የአዲስ አበባ ከተማ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት፣ የአዲስ አበባ ሰበታ ሜኤሶና የሜኤሶ ደዋሌ ፕሮጀክቶች የባቡር ግንባታዎች በቻይና የሃዲድ ግንባታ ደረጃ 2 እየተሰሩ መሆናቸው ቢገለጽም ተቋራጮቹ የጥራት ማረጋገጫ ማኑዋል፣ የላብራቶሪ ቁሳቁስ ማኑዋልና የዋና ዲዛይኑን ሰነድ የእንግሊዝኛ ትርጉም ለማቅረብ ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ ኮርፖሬሽኑ አገራዊ የባቡር ምህንድስና እና የዲዛይን ኮዶች አዘጋጅቶ ተግባራዊ ማድረግ ሲገባው የተለያዩ የውጭ አገር የባቡር ስታንዳርዶችን የተከተሉ የዲዛይንና ግንባታ ስምምነቶችን መፈረሙም በሪፖርቱ ላይ ተጠቁሟል፡፡ በኮርፖሬሽኑ እየተተገበሩ ያሉት የመሠረተ ልማት ግንባታዎች በ1999 ዓ.ም በትራንስፖርት ሚኒስቴር መሪነት አጥኚ ግብረሃይል ተቋቁሞ፣ አማራጭ የየብስ ትራንስፖርትን አስመልክቶ ያደረገው ጥናት እንጂ እያንዳንዱን ፕሮጀክት አስመልክቶ የተሰራ የፕሮጀክት ጥናት ሰነድ እንደሌለም ተገልጿል፡፡ በሜኤሶ ደዋሌ የባቡር መስመር ግንባታ ላይ ያለውን የእሳተ ገሞራ መከሰት ሁኔታ ሊገመግም የሚችል ጥናት አለመደረጉን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ኮርፖሬሽን እ.ኤ.አ በ2011 ከቻይናው ተቋራጭ (CCECC) ጋር ባደረገው ውል፣ ተቋራጩ ባቀረበው የቴክኒክ ፕሮፖዛል ውስጥ በምስራቅ አፍሪካ ያለው የእሳተ ጐሞራ በዓመት 0.5 ሳ.ሜ እንደሚሰነጠቅ ጠቁሞ ይህ ትልቅ ስምጥ ሸለቆ አሁንም
እየተሰነጠቀ መሆኑንና በዚህ ምክንያትም በላይኛው የምድር አካባቢ ያለው ክፍል ላይ ከፍተኛ እንቅስቃሴ መኖሩን፣ በተደጋጋሚ ፍንዳታዎችና የመሬት መሰንጠቆች እየተከሰቱ እንደሆነና ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ በዝርዝር የተጠናና የሚታወቅ ነገር ባለመኖሩ የእሳተ ጐሞራ መከሰት ሁኔታን አስተማማኝ ለማድረግ አለመቻሉን ኦዲት ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል፡፡ በኮርፖሬሽኑ እየተተገበሩ ባሉ ፕሮጀክቶች፣ የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ ተግባራዊ እየተደረገ አይደለም ያለው ሪፖርቱ፤ በአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ በርካታ የቱሪስት መተላለፊያ መንገዶችን ሳያስፈቅዱ መዝጋት፣ የፓርኩን ንፅህና አለመጠበቅ ያለፈቃድ መንገዶችን በፓርኩ ውስጥ እየቀደዱ ማውጣት የመሳሰሉ ችግሮች እንደሚከሰቱ ጠቁሞ በፕሮጀክቶቹ ላይ የሚሰሩ የውጪ አገር
ባለሙያዎች የዱር እንስሳትን ያለፈቃድ እያደኑ ለምግብነት እንደሚያውሉም ገልጿል፡፡  

Published in ዜና

መኖሪያ ቤታቸውን በ15 ቀን ውስጥ እንዲለቁ ታዘዋል

 “እኔ ሣላውቅ በስሜ በታተመ መፅሃፍ ሃሳቤን ተዘርፌያለው” ያሉት የፍልስፍና ምሁሩ ዶ/ር ዳኛቸው አሠፋ፤ መብቴን ለማስከበር በፍ/ቤት ክስ እመሰርታለሁ አሉ፡፡ መሐመድ ሀሰን በተባለ ፀሐፊ አማካኝነት “የዳኛቸው ሃሳቦች” በሚል ርዕስ ታትሞ በ80 ብር እየተሸጠ ነው የተባለው መፅሃፍ፤ ላለፉት 7 ዓመታት በተለያዩ የስልጠና መድረኮች፣ በሬዲዮ፣ በጋዜጦችና መፅሄቶች ያቀረቧቸው ሃሳቦች መሆናቸውን የጠቆሙት ምሁሩ፤ የመጽሐፉ አዘጋጅ “ትንታኔ” የሚል ቁንፅል አረፍተ ነገሮችን እየጨመረ ሃሳቦቼን ገልብጦ አትሞታል ሲሉ ከሰዋል፡፡ በመፅሃፉ ውስጥ ያሉት ሃሳቦች በሙሉ በ7 አመታት ውስጥ የተናገርኳቸው ናቸው ያሉት ዶ/ር ዳኛቸው፤ ግጥሞቹ ሳይቀሩ የራሳቸው እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ መፅሃፉ በግልፅ የኔን ሃሳብ በመዝረፍ የተዘጋጀ ነው የሚሉት ዶ/ሩ፤ “ከህግ ባለሙያዎች ጋር ተማክሬ በፍ/ቤት ካሣ እጠይቅበታለሁ፤ ይህን መሰል የሃሳብ ዝርፊያ እንዳይፈፀምም ለሌላው መቀጣጫ እንዲሆን እፈልጋለሁ” ብለዋል፡፡”
መፅሀፉ የታተመበት ማተሚያ ቤት አይታወቅም የሚሉት ምሁሩ፤ የኔን ፎቶግራፍ ለጥፎ፣ ‹የዳኛቸው
ሃሳቦች› ብሎ ማውጣት ትልቅ ወንጀል ነው ሲሉ ወቅሰዋል፡፡ዶ/ር ዳኛቸው፤ የራሳቸውን መፅሃፍ ለማሳተም ከአሳታሚዎች ጋር ተዋውለው እንደነበር ጠቁመው የዚህ መፅሀፍ በስማቸው መውጣት ሊያሳትሙ ባቀዱት መፅሃፍ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡በሌላ በኩል ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ፤ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መባረራቸውን ተከትሎ ላለፉት 7 ዓመታት ዩኒቨርሲቲው ሰጥቷቸው ይኖሩበት የነበረውን መኖሪያ ቤት በ15 ቀን ውስጥ ያለባቸውን 3300 ብር ውዝፍ እዳና የመብራትና ውሃ አገልግሎት ክፍያ ፈፅመው እንዲለቁ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ባለፈው ግንቦት 28 በፃፈላቸው ደብዳቤ ያስታወቀ ሲሆን ዶ/ር ዳኛቸው በበኩላቸው፤ በዩኒቨርሲቲው ያስተማሩበትንና የምርምር ስራዎች የሰሩበትን ወደ 56 ሺህ ብር ክፍያ ቢፈፀምላቸው እዳቸውን ከፍለው መልቀቅ እንደሚችሉ ጠቁመው የተሰጣቸው የጊዜ ገደብም በቂ አለመሆኑን ገልፀዋል - ለዩኒቨርሲቲው በደብዳቤ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡   

Published in ዜና

በጎተራ የሚገነባው መንደር 4 ቢሊዮን ብር ተመድቦለታል
           ሲኖማርክ የተባለው የሪልስቴት አልሚ ኩባንያ፤ በኢትዮጵያ ትልቁን የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት በአዲስ አበባ ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ። ኩባንያው በ4 ቢሊዮን ብር ወጪ ጎተራ አካባቢ ሊያስገነባው ያቀደው የሪልስቴት መንደር “ሮያል ጋርደን” የሚል ስያሜ ያለው ሲሆን፣ እያንዳንዳቸው 20 ወለሎች ያሏቸው 14 ህንፃዎች እንደሚኖሩት የኩባንያው ማርኬቲንግ ማኔጀር አቶ ተስፋዬ ገ/የሱስ ተናግረዋል፡፡
ጥራታቸውን የጠበቁ ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለኢትዮጵያውያን የማቅረብ አላማ
እንዳለው የገለጸው ኩባንያው፣ የሪልስቴት መንደሩ የመዋኛ ገንዳዎች፣ የህፃናት መጫወቻዎች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ማዕከላትና የንግድ ዞን እንደሚኖረውና አገር በቀሉ ሳባ ኢንጂነሪንግ በግንባታው ንደሚሳተፍበት አስታውቋል፡፡ሪል እስቴቱ የሚያስገነባቸው ህንፃዎች የየራሳቸው ሁለት ሁለት ሊፍቶች፣ ጀነሬተርና የውሃ ማጣሪያ ማሽኖች የሚኖራቸው ሲሆን የሪልስቴት መንደሩ ግንባታ በሶስት አመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተጠቁሟል፡፡ የቤቶቹ ዋጋ የፊታችን ሰኞ ይፋ ይደረጋል ተብሏል፡፡ ሲኖማርክ ሪልስቴት ላለፉት 7 አመታት በቻይናና በሌሎች አገራት የተለያዩ ታላላቅ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶችን በተሳካ ሁኔታ በማከናወን የሚታወቀው የቻይናው ሲንቹዋን ሄንግያንግ
ኢንቨስትመንት እህት ኩባንያ ነው፡፡

Published in ዜና

     መንግስት ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ከተፈጠረባቸው የመን፣ ሊቢያ እና ደቡብ አፍሪካ እስካሁን ወደ 4ሺህ ገደማ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ማድረጉን ገለጸ፡፡  የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከትናንት በስቲያ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ፤ በየመን ግጭት ከተፈጠረ ጊዜ አንስቶ ላለፉት ወራት፣ከ3800 በላይ ኢትዮጵያውያንን የጅቡቲና ሱዳን ኮሪደርን በመጠቀም ማስወጣት መቻሉን የጠቆመ ሲሆን 30 ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን በአይኤስ የሽብር ቡድን ከተገደሉባት ሊቢያ 140፣ እንዲሁም ጥቃት ይደርስብናል ብለው የሠጉ 45 ኢትዮጵያውያን ከደቡብ አፍሪካ ማስመለሱን አስታውቋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በየመን፣ ሊቢያና ደቡብ አፍሪካ ምን ያህል ስደተኛ ኢትዮጵያውያን እንዳሉ ባይገልጽም በየአገራቱ ባሉ የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽ/ቤቶችና ሚሲዮኖች አማካይነት በችግር ውስጥ
ያሉ ዜጐችን የማስመለሱ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክቷል፡፡ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ መስሪያ ቤት (UNHCR) በበኩሉ፤ በየመን ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ወደ 250ሺ የሚደርሱ የምስራቅ አፍሪካ ዜጐች በጦርነት ቀጠና ውስጥ እየተሰቃዩ እንደሚገኙ በቅርቡ ባወጣው መረጃ ጠቁሟል፡፡  
በሌላ በኩል ከነሐሴ 6-10 2007 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ የኢትዮጵያውያን የዳያስፖራ ቀን እንደሚከበር የተገለፀ ሲሆን በበአሉ ላይ በተለያዩ የአለም ክፍሎች የሚገኙ/ በሺዎች የሚገመቱ ኢትዮጵያውያን ይሳተፋሉ ተብሎ ተጠብቋል፡፡ የበአሉ አላማ ዳያስፖራዎች ስለ ሀገራቸው ወቅታዊ ሁኔታ በቂ መረጃ እንዲያገኙ፣ ዳያስፖራው በሀገሩ ጉዳይ ተሣታፊ እንዲሆንና ከሃገሩ ጋር ያለው ትስስር ይበልጥ እንዲጠናከር ለማስቻል ነው ያሉት ቃል አቀባዩ አቶ ተወልደ፤ በእለቱም የፓናል ውይይቶች፣ የስፖርት ዝግጅቶችና የጉብኝት ፕሮግራሞች ይከናወናሉ ብለዋል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚከበረውን በአል ለማሳለጥም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የበላይነት የሚመራ ኮሚቴ ተዋቅሮ ከወዲሁ አስፈላጊ ዝግጅቶችን እያደረገ መሆኑ
ተጠቁሟል፡፡  የዳያስፖራ ቀን በዓል ከመከበሩ ቀደም ብሎ በሃምሌ ወር፣ አዲስ አበባ አለማቀፍ የልማት ፋይናንስ ጉባኤን እንደምስታስተናግድም ተነግሯል፡፡ የጉባኤው አላማ ከ2015 የልማት ግብ በኋላ ለተቀረፁ የልማት ዘርፎች ገንዘብ ማፈላለጊያ መንገዶች ላይ ለመምከር መሆኑን የጠቆሙት ቃል አቀባዩ፤ በጉባኤው ላይ ከ5ሺህ በላይ ተሣታፊዎችና ከ200 በላይ የሚዲያ ሰዎች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ በጉባኤው ላይ የአገራት ፕሬዚዳንቶች፣ የአለማቀፍ ኩባንያ ባለቤት መሪዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እንደሚሳተፉ ታውቋል፡፡

Published in ዜና

       ጆቫጎ የተሰኘው አለማቀፍ የመንገደኞች የሆቴል ቀጠሮ አስያዥ ድረገጽ ከውጭ አገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ፣ ወደ ውጭ አገራት የሚጓዙና በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ መንገደኞችን በተመለከተ የሰራውን ጥናት ይፋ ማድረጉን ሜል ኤንድ ጋርዲያን ከትናንት በስቲያ ዘገበ፡፡በውጭ አገራት የሚኖሩ ትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በርካታ አለማቀፍ መንገደኞች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚጓዙ የጠቆመው ጥናቱ፣ ወደ ኢትዮጵያ በርካታ መንገደኞች የሚመጡባቸው ቀዳሚዎቹ አምስት አገራት አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ጀርመን፣ ደቡብ አፍሪካና ኬንያ ናቸው ብሏል፡፡  ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ጎብኝዎች ቁጥር ባለፉት አምስት አመታት ከፍተኛ እንደነበር የገለጸው ጥናቱ፣ እ.ኤ.አ በ2010 በድረ ገጹ አማካይነት በኢትዮጵያ የሆቴል ቀጠሮ ያስያዙ መንገደኞች 468 ሺህ እንደነበሩና ይህ ቁጥር በ2013 ወደ 681 ሺህ ከፍ ማለቱን ገልጾ፣ ቁጥሩ እስከ 2017 ከ1.2 ሚሊዮን በላይ እንደሚደርስ ያለውን ግምት አስቀምጧል፡፡ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት በድረገጹ አማካይነት የሆቴል ቀጠሮ ካስያዙ መንገደኞች፣ በከፍተኛ ርቀት ላይ የተገኘው የጃፓኗ ቶክዮ ከተማ መንገደኛ እንደነበርና ቀጠሮውን ያስያዘው በ10ሺህ 89
ኪሎሜትሮች ርቀት ላይ ሆኖ እንደነበር ጠቁሟል፡፡ በድረገጹ በኩል ቀጠሮ አስይዘው ወደተለያዩ አገራት የሚሄዱ ኢትዮጵያውያን መንደገኞችን በተመለከተም፣ ኢትዮጵያውያን መንገደኞች በብዛት የሚሄዱባቸው አገራት ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ አይቬሪኮስት፣ ጅቡቲና የተባበሩት አረብ ኢሜሬትስ ናቸው ብሏል ጥናቱ፡፡
በአገር ውስጥ የሚደረገውን የመንገደኞች ዝውውር በተመለከተም፣ አዲስ አበባ ከአገሪቱ ከተሞች በአገር ውስጥ መንገደኞች መዳረሻነት ቀዳሚነቱን መያዟንና ከመንገደኞቹ መካከል 13 በመቶ ሽፋን እንዳላት የገለጸው ጥናቱ፤ ጎንደር በ10 በመቶ፣ ላሊበላ በ9 በመቶ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን እንደያዙ ጠቁሟል፡፡ ከሃገር ውስጥ ጎብኝዎች 6 በመቶ የሚሆኑት ሃዋሳን ምርጫቸው አድርገዋል  ብሏል፡፡ ወደ ሌሎች የአገሪቱ ከተሞች በመጓዝ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች 60 በመቶውን ሲይዙ፣ የሃዋሳ ነዋሪዎች 2 በመቶ፣ የተቀሩት የአገሪቱ ከተሞች ደግሞ 38 በመቶውን ድርሻ ይይዛሉ ተብሏል፡፡

Published in ዜና

     በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን÷ ከሙስና እና ብልሹ አሠራር መንሰራፋት፣ ከመልካም  አስተዳደር እና ፍትሕ ዕጦት፣ ከአስተምህሮ እና ሥርዐት መጠበቅ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት እና በየሰንበት ት/ቤቶች መካከል የተቀሰቀሰው ውዝግብ እንደቀጠለ ነው፡፡
በሀገረ ስብከቱ ገዳማትና አድባራት÷ ሌቦች እየተበራከቱ፣ ጎጠኝነት እየተስፋፋ፣ በመናፍቅነታቸው የተወገዱ ግለሰቦች ተመልሰው እየተቀጠሩና አስተምህሮውን እየተፈታተኑ መሆናቸውን ሰንበት ት/ቤቶቹ ይገልፃሉ፡፡ ‹‹ሕገ ወጥ ሰዎችን አልደግፍም›› የሚለው ሀገረ ስብከቱ በበኩሉ፤ ካህናት ሙሰኞች ናቸው  ብሎ ንደማያምን ጠቁሞ፤ ‹‹ሰዎችን ሰረቃችሁ ለማለት ማስረጃ ያስፈልጋል›› ብሏል፡፡በሀገረ ስብከቱ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ የሚመሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሰንበት ት/ቤት አባላት፣ ባለፈው ማክሰኞ ከሀገረ ስብከቱ የሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ አባላት ጋር በሀገረ ስብከቱ ይፈፀማል በተባለው ብልሹ አሠራር ላይ ያካሄዱት ውይይት ባለመግባባት ተቋጭቷል፡፡ ሙስና እና ብልሹ አሠራርን በማጋለጣቸው ‹‹የፖሊቲካ ድርጅቶች ደጋፊዎች እና ሁከት ቀስቃሾች ናቸው፤ ፓትርያርኩን ይቃወማሉ›› በሚል እየታሰሩ እንደሆነ በውይይቱ ላይ የተናገሩት የሰንበት ት/ቤቶቹ፤ በሰሚት መካነ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን አሠራሩን የተቃወሙ በፖሊስ ጣቢያ ታስረው ክሥ እንደተመሠረተባቸው፤ ካህናትም የንስሐ አባት እንዳይኾኗቸው በደብዳቤ መመሪያ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡በሀገረ ስብከቱ ባለሥልጣናት የሚመኩና የጥቅም ትስስር ያላቸው የአድባራትና የገዳማት ሓላፊዎች ከሦስት እስከ አራት ሺሕ ብር ያልበለጠ ደመወዝ እየተከፈላቸው ውድ ዋጋ ያላቸውን መኪኖችን እንደሚነዱና ቤት እንደሚገዙ ጠቁመው ገንዘቡ ከየት እንደመጣ ሊጣራ ይገባዋል ብለዋል። ሀገረ ስብከቱ የሙዳዬ ምጽዋት ቆጠራ በካሽ ካውንተር እንዲከናወን ማድረጉን ቢደግፉም በፐርሰንት አከፋፈል፣ በቦታ እና በሕንፃ ኪራይ፣ በሠራተኞች ቅጥርና ዝውውር ረገድ በጥቅም ትስስር የሚፈጠሩ ችግሮች እንዲፈቱ፤ በየአጥቢያው የሚታየው የጎጠኝነት መከፋፈል መፍትሔ እንዲያገኝ
አበክረው ጠይቀዋል፡፡ ሰንበት ት/ቤቶቹ ለዘረዘሯቸው በርካታ ችግሮች  ምላሽ የሰጡት የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ ሰዎችን ሰረቃችሁ ለማለት ማስረጃ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ ‹‹ካህናት ሙሰኞች ናቸው ብለን አናምንም፤ መኪና ቢኖራቸው ቪላ ቤት ቢኖራቸው ደስ ይለናል፡፡ ካህናት የሀብት ችግር አለባቸው እንጂ ታማኞች ናቸው›› ሲሉ ተናግረዋል፤ ከሙዳይ ምጽዋት ጥገኝነት ይልቅ በልማት ሥራ መሠማራት እንደሚመረጥም አብራርተዋል፡፡ በሀገረ ስብከቱ የሠራተኛ ቅጥር እየተፈጸመ ያለው በውድድር እንደሆነና ለውጡ ባይጠናቀቅም መጀመሩ መልካም ነው ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ በቤተ ክርስቲያን ጎጠኝነትን ጨምሮ ሙስናን በሁለንተናዊ ገጽታው መዋጋት ይገባል ብለዋል፡፡

Published in ዜና
Page 11 of 16