- በብጥብጡ ከ70 በላይ ሰዎች ሞተዋል
ከሁለት አመታት በፊት አልማስሪ እና አልሃሊ በተባሉት የግብጽ እግር ኳስ ቡድኖች ደጋፊዎች መካከል በፖርት ሲቲ ስቴዲየም የተከሰተውንና ከ70 በላይ ሰዎች የሞቱበትን ብጥብጥ በማነሳሳት የተከሰሱ 11 ግብጻውያን የሞት ቅጣት እንደተጣለባቸው ሲ ኤንኤን ዘገበ፡፡
ባለፈው ማክሰኞ በካይሮ የተሰየመው ችሎት በግብጽ የእግር ኳስ ታሪክ አስከፊው የተባለለትንና ህጻናትን ጨምሮ ለህልፈተ ህይወት የተዳረጉበትን ይህን ብጥብጥ በማነሳሳታቸው የሞት ቅጣት ከጣለባቸው ከእነዚሁ 11 ግለሰቦች በተጨማሪ፣ በብጥብጡ ተሳትፈዋል ባላቸው ሌሎች 40 ሰዎች ላይም የእስር ቅጣት ጥሏል፡፡
ተመልካቾቹ እርስበርስ በድንጋይ፣ በካራና በገጀራ በአስከፊ ሁኔታ የተጨፋጨፉበት ይህ ከፍተኛ ብጥብጥ መከሰቱን ተከትሎ፣ ግብጽ የእግር ኳስ ደጋፊዎች ስታዲየም እንዳይገቡ እገዳ መጣሏንና ጨዋታዎች በዝግ ስቴዲየም ሲከናወኑ መቆየታቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ በሂደትም የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ተመልካቾች ብቻ ወደ ስቴዲየም እንዲገቡ መፈቀዱን ገልጧል፡፡
በግብጽ ከዚያ በኋላም የእግር ኳስ ደጋፊዎች ብጥብጥ መከሰቱን የጠቆመው ዘገባው፣ ባለፈው የካቲት ወር ላይም የዛማሌክ እግር ኳስ ክለብ ደጋፊዎች ባስነሱት ብጥብጥ 19 ሰዎች ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውን አክሎ ጠቁሟል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

      የዓለም ጤና ድርጅት ለመድሃኒት በሰጠው ትርጓሜ መሰረት፤ መድሃኒቶች ለህመምተኞች በሚስማማ መልኩ ተዘጋጅተው በሽታዎችን ለማከም፣ ለማስወገድና ለመከላከል የምንጠቀምባቸውና በፋብሪካ ተመርተው የሚወጡ ኬሚካሎች ናቸው፡፡ መድሃኒቶች በተፈጥሮአዊ ባህርያቸው የጐንዮሽ ጉዳትን የሚያስከትሉ ሲሆን ይህ የጐንዮሽ ጉዳታቸው እንደ መድሃኒቶቹ ዓይነትና የአወሳሰድ መጠን ሊለያይ እንደሚችል ያመለክታል። በዚህ ምክንያትም መድሃኒቶችን ለህመምተኞች የሚያዙ ሃኪሞችም ሆኑ መድሃኒቶችን ለተጠቃሚው የሚያድሉ ሙያተኞች (ፋርማሲስቶች)፤ መድሃኒቶቹ በህመምተኛው ላይ የሚያስከትሉትን አላስፈላጊ ውጤትና የጐንዮሽ ጉዳቶቹን ለህመምተኛው በግልጽ ማሣወቅና፣ ህመምተኛው መድሃኒቱን ተገቢውን የአወሳሰድ ሥርዓት ተከትሎ መውሰድ እንደሚገባው በግልጽ መንገር ይኖርባቸዋል፡፡
በአገራችን ያለው የመድሃኒት አጠቃቀም በአብዛኛው ትክክለኛ ሥርዓትን ያልተከተለና ጤናማ አለመሆኑ ከመድሃኒቶቹ የጐንዮሽ ጉዳቶች ጋር ተዳምሮ በርካቶችን ለከፋ የጤና ችግር እንደሚያጋልጣቸው የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ሃኪም ዶ/ር ተስፋዬ ሽፈራው ስለዚህ ጉዳይ ሲያስረዱ፤ “ህብረተሰቡ መድሃኒትን በአግባቡ የመጠቀም ልምድ የለውም፤ በአግባቡና በሥርዓቱ ያልተወሰዱ መድሃኒቶች የሚያስከትሉትን የከፋ የጤና ችግር በሚገባ ተረድቷል ማለትም አይቻልም፡፡ በመንግስትም ሆነ በግል የጤና ተቋማት ውስጥ ያሉ የጤና ባለሙያዎችም ሆኑ በመድሃኒት እደላ (ሽያጭ) ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች ስለትክክለኛ የመድሃኒት አጠቃቀምና መድሃኒቶች ስለሚያስከትሉት የጐንዮሽ ጉዳት ለህመምተኞቹ በግልጽና በአግባቡ የማስረዳቱ ጉዳይ እጅግ ብዙ ይቀረዋል፡፡ አንዳንዴም በባለሙያዎቹ የጊዜ ማጣት ወይም በቂ ዕውቀት ካለመኖር የተነሳ ሊሆን ይችላል። ግን አንድ ህመምተኛ ስለሚወሰደው መድሃኒት ምንነት፣ መድሃኒቱ ስለሚያስከትለው የጐንዮሽ ጉዳት፣ አንዳንዴም ስለመድሃኒቱ ኬሚካላዊ ይዘት በባለሙያ በደንብ ሊነገረው ይገባል፡፡ መድሃኒቱን በተገቢው ሰዓትና መጠን መውሰዱ ከምን ሊያድነው እንደሚችል ማስረዳትም ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡
“አግባብ ያልሆነ የመድሃኒት አጠቃቀም ህይወትን ለአደጋ የሚያጋልጥና የከፋ የጤና ችግር የሚያስከትል መሆኑንም እንዲያውቅ መደረግ ይገባዋል” ብለዋል ሃኪሙ፡፡
መድሃኒቶች በተለያዩ አገራት ተሠርተው የተለያዩ ስምና ብራንዶች እየተሰጣቸው ወደ አገር ውስጥ እንደሚገቡ የሚናገሩት ዶክተሩ፤ በእነዚህ መድሃኒቶች የመፈወስ አቅም ላይ ተጠቃሚዎች በየጊዜው የሚያነሷቸው ጉዳዮች እንዳሉና በአብዛኞቹ እንደማይስማሙባቸው ጠቁመዋል፡፡
አንድ መድሃኒት የቤተሙከራ ዘመኑን ጨርሶ ጥቅም ላይ እንዲውል እስከሚደረግበት ጊዜ ድረስ ቢያንስ ከ10-15 ዓመታት እንደሚፈጅበት የሚናገሩት ሃኪሙ፤ የመድሃኒቱ ፈጣሪ ኩባንያ መድሃኒቶቹ ተመርተው ገበያ ላይ ከዋሉበት ጊዜ ጀምሮ ቢያንስ ለ15 ዓመታት የሚቆይ የባለቤትነት ማረጋገጫ ይሰጠዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥም ኩባንያው ከሌሎች የመድሃኒት አምራች ኩባንያዎች ጋር ተስማምቶ፣ መድሃኒቱን በራሳቸው የቅመማ ሂደት ደረጃውን ጠብቀው እንዲያመርቱ ፈቃድ ይሰጣቸዋል፡፡ በዚህ ፈቃድ መሰረትም ኩባንያዎቹ  የመድሃኒቱ ፈጣሪ ኩባንያ ከሚሰራው መድሃኒት ጋር ተመሳሳይ ይዘት ያላቸውን መድሃኒቶች እያመረቱ የራሳቸውን ስምና ብራንድ በመስጠት ገበያ ላይ ያውሉታል፡፡ በፈዋሽነታቸውም ሆነ በይዘታቸው ተመሳሳይ የሆኑ መድሃኒቶች በተለያዩ ስምና ብራንዶች ለተጠቃሚው ይደርሳሉ ማለት ነው፡፡ የእነዚህ መድሃኒቶች የፈውስ አቅም ታዲያ አንድ አይነት ነው፡፡ የመድሃኒቶቹ ዋጋ ከፍና ዝቅ ማለት ጋር ከመድሃኒቶቹን ጥራትና የመፈወስ አቅም ጋር ማያያዙ ተገቢ የሆነ አመለካከት አይደለም፡፡
መድሃኒቶቹ እንደሚመረቱበት አገር የታክስና የማምረቻ ቁሳቁስ ዋጋ እንዲሁም የሠራተኛ ክፍያ ዋጋቸው ከፍና ዝቅ ሊል ይችላል፡፡                 
መድኀኒቶች ወደ አገር ውስጥ ከመግባታቸው በፊትም ሆነ በአገር ውስጥ ገብተው ለተጠቃሚው ከመድረሳቸው በፊት በመድኀኒቶቹ ጥራትና በመጠቀሚያ ጊዜያቸው ላይ የሚደረጉ ቁጥጥሮችን አስመልክተው ሲናገሩም በአገራችን የመድኀኒት አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን እንደዚህ አይነት ጉዳዮችን የመቆጣጠር ኃላፊነት እንዳለበት ጠቁመው መድኀኒቶች ወደ አገር ውስጥ ከመግባታቸው በፊትም ሆነ ገበያ ላይ ከማዋላቸው በፊት የመድኀኒቶቹን ጥራትና ፈዋሽነት ለማረጋገጥ በቤተ ሙከራ ፍተሻ ያደርጋሉ፡፡ መድኀኒቶች የህንን አሰራር ተከትለው ካልሆነ በስተቀር ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ አይፈቀድም፡፡ ይሁን እንጂ መድኀኒቶች ወደ አገር ውስጥ ገብተው በተለያዩ መንገዶች ለህብረተሰቡ እንዲዳረሱ ሲደረግ የሚደረግ ክትትልና ቁጥጥር የለም፡፡ መድኀኒቶቹ ከተሰራጩ በኋላ በድንገት ገበያ ውስጥ በመግባትና ሳምፕሎችን (ናሙናዎችን) በመውሰድ ተገቢ ምርመራና ቁጥጥር ማድረግ እምብዛም የተለመደና እየተሰራበት ያለ ጉዳይ አይደለም፡፡ በችርቻሮ ስራ ላይ የተሰማሩ መድኀኒት ሻጮችና አከፋፋዮች የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸውን መድኀኒቶች ከገበያ ለማስወገድ ጥረት ሲያደርጉ አይታዩም። ይህ ታዲያ ህብረተሰቡን ለከፍተኛ አደጋ የሚያጋልጥና በመድኀኒት አጠቃቀም ሥርዓት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን የሚያስከትል ነው፡፡ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ይህን መሰሉን ለአገርና ለህዝብ አደጋ የሆነ ችግር በጋራ ለማስወገድ ጥረት ማድረግ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ መድኀኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የመድኀኒት አቅርት፣ አግባብ ያልሆኑ የመድኀኒት አጠቃቀሞችንና የሚያስከትሉትን የጤና ችግሮች አስመልክቶ በአዳማ ከተማ ሰሞኑን ለጋዜጠኞች አንድ የግንዛቤ ማስጨበጫ አውደጥናት አዘጋጅቶ ነበር፡፡ በዚህ አውደ ጥናት ላይ የኤጀንሲው የግዥ ትንበያና አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ይገዙ እንደተናገሩት፤ አግባባዊ ባልሆኑ የመድኀኒት አጠቃቀም ችግሮች ሳቢያ በተጠቃሚዎች ላይ የሚደርሱ ከፍተኛ የጤና ችግሮች አሉ፡፡ ኤጀንሲው በአገሪቱ ዋና ዋና የጤና ችግሮች ላይ ያተኮሩ፣ ጥራታቸው የተረጋገጠ መሰረታዊ መድኀኒቶችን በበቂ መጠን፣ በተመጣጣኝ ዋጋና ቀጣይነት ባለው መልኩ እያቀረበ ለመንግስትና የግል የጤና ተቋማት የሚያሰራጭ መሆኑን ጠቁመው እነዚህን መድኀኒቶች በተገቢው መንገድ፣ በተፈላጊው መጠንና ሁኔታ በመውሰድ አግባብ ባልሆነ መንገድ በመውሰድ ከሚከሰቱ የጤና ችግሮች ህብረተሰቡ ራሱን ሊጠብቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡በዚሁ አውደ ጥናት ላይ ጥናታዊ ፅሁፋቸውን ያቀረቡት የኤጀንሲው የግዢ ትንበያና አቅም ግባታ ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ሲራጅ አደም በበኩላቸው፤ ኤጀንሲው መድኀኒቶችን እየገዛ በአገሪቱ ባሉት የተለያዩ ቅርንጫፎቹ አማካኝት የሚያከፋፍል መሆኑን ጠቁመው የመንግስትም ሆነ የግል የጤና ተቋማት መድኀኒቶች በተገቢው ጊዜ እንዲደርሳቸው በማድረጉ ረገድ ኤጀንሲው ከፍተኛ ስራ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡ በአገሪቱ የሚገኙ ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች መድኀኒቶችን ይዘው ለማቆየት የሚችሉባቸው ጊዜያት ውስን መሆኑን የጠቆሙት እኚሁ ፅሁፍ አቅራቢ ከሁለት እስከ አራት ወር በሚደርሱ ጊዜያት መድኀኒቶች በጤና ተቋማት ውስጥ መቆየት እንደሚችሉና ከዚህ ጊዜ በላይ መድኀኒቶችን በየጤና ተቋማቱ ማቆየቱ ለብልሽት ሊዳርግ እንደሚችልም ገልፀዋል። ኤጀንሲው በአዳማ ከተማ ውስጥ የሚገኘውን ቅርንጫፍ የመድኀኒት ማከማቻና ማከፋፈያ መጋዘኑንም ለጋዜጠኞቹ አስጎብኝቷል፡፡ ይህ ቅርንጫፍ መጋዘን በቅርቡ የቃጠሎ አደጋ ደርሶበት እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸውና እስከአሁን በገንዘብ ሊተመኑ ያልቻሉ መድኀኒቶችና የህክምና መገልገያ ቁሳቁሶችን በቃጠሎው አጥቷል፡፡ የቅርንጫፍ መ/ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ አየለ ታደሰ በቃጠሎው አደጋ ምክንያት በመጋዘኑ ላይ የደረሰውን ጉዳት አስመልክቶ ዝርዝር ማብራሪያ ለመስጠት አልቻሉም፡፡ ምርመራው ተጠናቆ እንዳልደረሳቸውና የተቃጠለውን የመድኀኒት መጠንም ለማወቅ ጊዜው ገና መሆኑን በዚሁ የጉብኝት ወቅት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡                        

Published in ዋናው ጤና

      ከትናንት በስቲያ በድምቀተ የተከፈተው 3ኛው ሆቴል ሾው ኢትዮጵያ 2007 የሆስፒታሊቲ ቱሪዝም ፎረምና ኤክስፖ ነገ ይዘጋል ሲሉ የኦዚ ቢዝነስና ሆስፒታሊቲ ግሩፕ መስራችና ማኔጂንግ ዳይሬክተር አስታወቁ፡፡
ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ አቶ ቁምነገር ተከተል በተለይ ለጋዜጣው ሪፖርተር በሰጡት መግለጫ፤ ነገ ለአካባቢ ጥበቃ የሚቆረቆሩና የሚጨነቁ ሆቴሎች ተወዳድረው አሸናፊውን በመሸለም የንግድ ትርኢትና ኤክስፖው ይዘጋል ብለዋል፡፡
ለሦስተኛ ጊዜ ከሰኔ 4 ጀምሮ በሚሊኒየም አዳራሽ ሲካሄድ የቆየው የንግድ ትርኢትና ኤክስፖ  ዓላማ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው፣ በአፍሪካ ታዋቂ የሆነና በኢትዮጵያዊ ባህላዊ መሠረት ላይ የተገነባ የሆስፒታሊቲና የቱሪዝም መድረክ መፍጠር ነው ያሉት አቶ ቁምነገር፤ ባለድርሻ አካላት መድረክ ፈጥረው በዓለም አቀፍ መስፈርት መሰረት በአገር ውስጥ የሚታዩ ኢንዱስትሪ ነክ ጉዳዮችን ለመዳሰስ፣ አዳዲስ አሰራሮችን ለመጋራትና ለልምድ ልውውጥ አመቺ ሁኔታ መፍጠር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በ3ኛው ሆቴል ሾው ኢትዮጵያ ከኢጣሊያ፣ ፈረንሳይ፣ ዩ.ኤስ.ኤ፣ ታይላንድ፣ ቱርክ ደቡብ አፍሪካ፣ ግብፅ፣ ዱባይና ቻይና የመጡ 145 አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶች፣ የቢዝነስ ሀሳቦች (አይዲያ) የያዙና የገበያ አፈላላጊ ኩባያዎች እየተሳተፉ እንደሆነ ታውቋል፡፡
በንግድ ትርኢትና ኤክስፖው ላይ ሁለት ጥናታዊ ጽሁፎች እንደሚቀርብ የጠቀሱት ማኔጂንግ ማናጀሩ፣ ትናንት ቤልጂየማዊው የ “ሄድ ኳተር ማጋዚን” ማኔጂንግ ዳይሬክተር፣ የኢትዮጵያን የሆስፒታሊቲ ኢንዱስትሪ ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር በሚል ርዕስ ጥናታዊ ፅሑፍ ማቅረባቸውን፣ ዛሬ ደግሞ ደቡብ አፍሪካዊው የቢዝነስ ቱሪዝም  ኩባንያ ፕሬዚዳንት፤ የኢትዮጵያ የስብሰባ የኢንሼዬንቲቭ፤ (ኮንፈረንስ፣ ኤግዚቢሽን ወይም ኤቨንት) እምቅ የቱሪዝም ገበያ ዕድሎችና አጠቃቀማቸው በሚል ርዕስ ጽሑፍ ያቀርባሉ፡፡ እስካሁን በኢትዮጵያ ስብሰባዎች የሚካሄዱት በመንግስት አዘጋጅነት ብቻ ሳይሆን ቢዝነሱ ራሱ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት እንዳለበት ጠቅሰው፤ ለምሳሌ ቢልጌት 2 ሚሊዮን ዶላር መድቦ በኤድስ ላይ ዓለም አቀፍ ጉባኤ እንዲያዘጋጅ ዕድሉ ለግል ኮንፈረንስ አዘጋጅ ድርጅቶች ቢሰጥ፣ የአዘጋጅቱን ኃላፊነት የወሰደው ድርጅት በኤድስ በብዛት የተጎዳችው አፍሪካ ስለሆነች ስብሰባውን በአፍሪካ ለማድረግ ወስኖ በየትኛዋ አገር ይካሄድ? ብሎ ሲፈልግ፣ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ማዘጋጀት እንደምትችል ታውቆ ከቢዝነሱ የሚገኘው ገቢ (ማይስ MICE) መጠቀም በምትችልበት አሰራር ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀርባሉ ብለዋል፡፡  የንግድ ትርኢቱና ኤክስፖው በተከፈተበት ሥነ-ሥርዓት በሚቀጥለው ዓመት በመጋቢት ወር ስራ የሚጀምረው የስብሰባ፣ ኢንሴንቲቭ፣ ኮንፈረንስ (ኮንግረስ) ኤግዚቢሽን (ኢቨንት) አዘጋጅ ማይስ MICE ምሥራቅ አፍሪካ 2008 ፎረምና ኤክስፖ መቋቋሙን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ሚኒስትር ክቡር ሬድዋን ሁሴንና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተወካይ አቶ ተወልደ ወ/ማርያምን በመወከል አቶ ኢሳያስ ወ/ማርያም ይፋ አድርገዋል፡፡
ነገ ቨ3ኛው ሆቴል ሾው ኢትዮጵያ 2007 የንግድ ትርኢትና ኤክስፖ ከመዘጋቱ በፊት በተለያዩ ሆቴሎችና ሪዞርቶች መካከል የሙያ ውድድርና የልምድ ለውውጥ እንደሚካሄድ፣ እንዲሁም በዲዛይንና ግንባታ ወቅት ለአካባቢ ጥበቃ ክብካቤ ከፍተኛ ትኩረት በሰጡ ሆቴሎችና ሪዞርቶች መካከል ውድድር ተካሂዶ አሸናፊዎቹ እንደሚሸለሙ አቶ ቁምነገር ተከተል አስታውቀዋል፡፡  

ኮካኮላ ኢትዮጵያ ከተለያዩ የአዲስ አበባ ት/ቤቶች ከተውጣጡ 50 ታዳጊ ተማሪዎች ጋር “በራስ ለመተማመን ቢሊዮን ምክንያቶች አሉን” በሚል መርህ ባለፈው ረቡዕ በሻላ መናፈሻ ዘመቻ ጀመረ፡፡
“በራስ ለመተማመን ቢሊዮን ምክንያቶች” በሚል መሪ ቃል ኮካኮላ በመላው አፍሪካ የጀመረው ዘመቻ አካል ሲሆን ዓላማውም ወጣት አርቲስቶች የተለያዩ ችግሮችን አልፈው ለስኬት የበቁበትን ተሞክሮ ለታዳጊዎች በማካፈል የአህጉሩን ቀና አስተሳሰብና አስደናቂ ታሪኮች በመሰብሰብ፣ የአፍሪካን ልዩ ታሪኮች ለማክበር መንገድ መክፈት እንደሆነ የኮካኮላ ኢትዮጵያ ማናጀር ሚ/ር ኬንጐሪ ማቻሪያ ገልፀዋል፡፡
ድርጅቱ ከተለያዩ የሕይወት ዘርፎች አራት ተፅዕኖ ፈጣሪ አርቲስቶች ያጋጠሟቸውን ፈታኝ ችግሮች እንዴት አልፈው ለስኬት እንደበቁ ለኢትዮጵያ ታዳጊዎች እንዲያካፍሉ የመረጠ ሲሆን እነሱም በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያተረፈችው ዲዛይነር ማኅሌት አፈወርቅ (ማፊ)፣ በኢትዮጵያ የሬጌ አልበም ያወጣው ስኬታማ ሙዚቀኛ ዮሐንስ በቀለ (ጆኒራጋ) ከፍተኛ እውቅና ካላቸው ሴት ዲጄዎች አንዷ የሆነችው የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ማርሼት ፍሰሐ (ዲጄ የሚ) እና አካል የሚያደክም በሽታ ቢኖርበትም በፅናት ተቋቁሞ ለስኬት የበቃውና በአነቃቂ ንግግሮቹ የሚታወቀው ሰዓሊ ብሩክ የሺጥላ ናቸው፡፡
በዝግጅቱ ወቅት ታዳጊዎች በተለያዩ ምድቦች ተከፋፍለው እንዲሁም በግለሰብ ደረጃ ከተፅዕኖ ፈጣሪዎቹ ዝነኞቹ ጋር ተነጋግረዋል፡፡ ይህም ታዳጊዎች ውጤታማ አርአያ ሞዴሎች ለማግኘት ልዩ ዕድል የፈጠረላቸው ከመሆኑም በላይ የሥራ ፈጠራ፣ ከባድ ሥራ፣ የሕይወት ተድላና ስኬት በቀላሉ እንደማይገኝ የሚያሳይ እውነታ ተምረውበታል ብለዋል የኮካኮላ ኃላፊ፡፡

በአዲስ አበባ 36ሺ የምግብ ድጋፍ የሚፈልጉ ህፃናት አሉ
በአትሌት ኃይሌ ሚመራ “አንድ ልጅ ይርዱ” ቅስቀሳ ይጀመራል


አገር በቀሉ “ቪዥን ፎር ጀነሬሽን” መሥራችና የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ያሬድ ግርማ ከ4 ዓመት በፊት ለሥራ ጉዳይ ወደ ድሬዳዋ ሄዶ ነበር፡፡ በጨዋታ ጨዋታ “ለመማር ከፍተኛ ፍላጐት ያላቸውና የትምህርት አቀባበላቸውም በጣም ጥሩ የሆኑ ልጆች በመንግሥት አንደኛ ደረጃ ት/ቤት እየተማሩ ነው፡፡ እነዚህ ጐበዝ ልጆች ጥሩ እውቀት የሚያገኙበት ት/ቤት ቢማሩ የተሻለ እውቀት ቀስመው፣ የነገዋን ኢትዮጵያ ተረክበው የተጀመረውን ዕድገት ያፋጥኑ ነበር፡፡ ነገር ግን ጥሩ እውቀት የሚቀስሙበት ት/ቤት እንዳይማሩ የቤተሰቦቻቸው ድህነት እንቅፋት ሆነባቸው፡፡…” የሚል አሳዛኝ ነገር ሰማና ከልቡ አዘነ።
በአዲስ አበባ የጐስቋሎች መናኸሪያ በሆነችው ጨርቆስ አካባቢ ተወልዶ ያደገው አቶ ያሬድ፤ የድህነትን አበሳና ጠባሳ በሚገባ ያውቃል፡፡ አቶ ያሬድ ሰሞኑን በጽ/ቤቱ በሰጠው መግለጫ፤ “ሀብታም ሰው ሳናይ ነው ያደግነው፡፡ ቂርቆስ የተወለደ ልጅ ትምህርት የሚያገኘው በዕድል ነው።” ብሏል፡፡ በመላ አገሪቱ ከድሃ ቤተሰብ የተወለዱና የትምህርት አቀባበላቸው ከፍተኛ የሆነ በርካታ ልጆች እንዳሉ ያምናል፡፡ እነዚህ ልጆች ድጋፍ ቢያገኙ በቀሰሙት እውቀት አገራቸውን በማበልፀግ ውለታ መላሽ ይሆናሉ፡፡ ድጋፍ ካላገኙ የነበራቸውን ጥሩ የትምህርት አቀባበል ችሎታ አጥተው (ተነጥቀው) የአገርና የኅብረተሰቡ ሸክም ሲሆኑ ታየውና ከማኅበሩ አባላት ጋር የዜግነት ኃላፊነታቸውን ለመወጣት መንቀሳቀስ ጀመሩ፡፡
ችግሩን በግላቸው ብቻ መወጣት ስለማይችሉ፣ ደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠየቁ፡፡ ድርጅቱም በሐሳባቸው ተስማምቶ 100 ሺህ ብር ፈቀደላቸው፡፡ አቶ ያሬድ ወደ ድሬዳዋ ተመልሶ ከተለያዩ 5 የመንግሥት ት/ቤት ከፍተኛ የትምህርት አቀባበል ችሎታ ያላቸውን 12 የድሃ ቤተሰብ ልጆች ከ5ኛ፣ ከ6ኛ፣ ከ7ኛ ክፍል መርጦ፣ በድሬዳዋ እንደ አዲስ አበባው ቅዱስ ዮሴፍ በሚቆጠረው ኖተርዳም ካቶሊክ ት/ቤት አስገብቶ ለት/ቤቱና ለትምህርት መርጃ መሳሪያዎች ለዩኒፎርም በወር 1,000 ብር እየከፈሉ አስተማሩ፡፡
ልጆቹ ከአራት ልጆች ዓመት በኋላ ያስመዘገቡት ከፍተኛ ውጤት ጮቤ የሚያስረግጥ እንደሆነ አቶ ያሬድ በኩራትና በደስታ ገልጿል፡፡ አምና አራቱ የ10ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ወስደው ሦስቱ ልጆች ከፍተኛውን 4፡00 ማምጣታቸውን ተናግሯል። ልጆቹ ያመጡት ውጤት ከፍተኛ ሞራል ስለሰጠው፣ ከፍተኛ የትምህርት አቀባበል ያላቸውን የድሃ ቤተሰብ ልጆች ማስተማሩን ለመቀጠል አበረታታው፡፡
ነገር ግን አንድ ችግር ታየው፡፡ ልጆቹን ያስተማሩት በወር 1000 ብር እየከፈሉ ነበር፡፡ የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርግ ድርጅት ቢጠፋ ልጆቹ ትምህርታቸው ስለሚቋረጥ ለምን ት/ቤት አንሰራም? አሉ፡፡ እኛ እንጀምረውና ካልሆነልን ኅብረተሰቡ ይጨርሰዋል በማለት አዳሪ ት/ቤት ለመሥራት ተንቀሳቅሰው በጐንደር 20ሺህ ካ.ሜ ቦታ አገኙ፡፡  የት/ቤቱ ግንባታ 117 ሚሊዮን ብር ይፈጃል፡፡ ለት/ቤቱ ማሰሪያ በሸራተን ሆቴል የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም አዘጋጅተው፣ 10 ሚሊዮን ብር ቃል ተገብቶላቸዋል፡፡ ሌላ ችግር ደግሞ  ታያቸው፡፡ ለት/ቤቱ ግንባታ የሚያስፈልገው ገንዘብ እስኪሟላና ቃል የተገባውም እስኪሰበስብ ድረስ ብዙ ጊዜ ይፈጃል፡፡ በዚህ ሂደት ት/ቤት አሠርቶ ልጆቹን ተቀብሎ የማስተማር ዕቅዳቸው ብዙ ጊዜ ይቆያል። ከድሃ ቤተሰብ የሚወለዱ ልጆች አንዱና ዋነኛው ችግር የምግብ እጦት ስለሆነ ለምን ልጆቹ ባሉበት ት/ቤት እየተረዱ፣ እንዲማሩ ከቋሚ ድርጅቶች ጋር አናገናኝም? በማለት እንቅስቃሴ ጀመሩ፡፡
ዓላማቸውን የሚገልጽ ፕሮፖዛል አዘጋጅተው፣ ለመከላከያ ሚኒስቴር አስገቡ፡፡ ሚኒስትሩም ሐሳቡን በደስታ ተቀብሎ በአራዳና በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በሚገኙ 14 ት/ቤቶች የትምህርት አቀባበላቸው ከፍተኛ የሆኑ 315 ተማሪዎች ለመደገፍ በዓመት 1.4 ሚሊዮን ብር መደበ፡፡ ልጆቹ የምግብ አቅርቦቱን የሚያገኙት በሚማሩበት ት/ቤት መዝናኛ ክበብ ነው፡፡ በየቀኑ እንዲመገቡ ለአንድ ልጅ 12 ብር ለክበቡ ይከፍላሉ፡፡ ልጆቹ በትምህርታቸው ጥሩ ውጤት ካመጡ በመከላከያ ተቋማት ትምህርታቸውን ለማስቀጠል፣ ከዚህም በላይ በውጭ አገር ነፃ የትምህርት ዕድል (ስኮላርሺፕ) እንዲያገኙ ለማድረግ መ/ቤቱ ቃል ገብቷል፡፡ ሌላው በሐሳባቸው ተስማምቶ ሊደግፋቸው ቃል የገባው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው፡፡ አየር መንገዱ በቦሌ ክፍለ ከተማ የሚገኙ 150 የድሃ ቤተሰብ ልጆች ለመመገብ ተስማምቷል፡፡ ለዚህም ለአየር መንገዱ ለሠራተኞች የተዘጋጀውን ምግብ ከክበቡ እየወሰዱ በየት/ቤቱ የሚያደርሱ 5 ተሽከርካሪዎች የመደበ ሲሆን ምገባው ዛሬ እንደሚጀመር አቶ ያሬድ ገልጿል፡፡ ከምግቡ በተጨማሪ ተማሪዎቹ በትምህርታቸው ጥሩ ውጤት ካመጡ በአየር መንገዱ አካዳሚ ገብተው የመሠልጠንና የማገልገል ዕድል ለመስጠት ቃል ገብቷል፡፡ በቅርቡ በአትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ የሚመራ “አንድ ልጅ ይርዱ” የሚል ቅስቀሳ እንደሚጀመር አቶ ያሬድ ገልጿል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ 36‚000 የምግብ ድጋፍ የሚፈልጉ ሕፃናት እንዳሉ የጠቀሰው የድርጅቱ መስራችና የቦርድ ሰብሳቢ፤ የሁሉንም ሕፃናት የምግብ ችግር መፍታት ባይችሉም በ13 ዓመት (በኢትዮጵያ አቆጣጠር እስከ 2020 ዓ.ም) 10 ሺህ ሕፃናት፣ 1ኛ፣ 2ኛ እና የመሰናዶ ትምህርታቸውን እስኪጨርሱ እየመገበ እንደሚያስተምርና በአሁኑ ወቅት 470 እንደሚረዳ አስታውቋል፡፡
“ቪዥን ፎር ጀነሬሽን” ከ4 ዓመት በፊት ሲቋቋም የመጪው ትውልድ አገር ተረካቢ ሕፃናት ጥሩ አገር ኖሯቸው፣ አገር ወዳድ ዜጋ እንዲሆኑ ማስተማር ነበር ራዕዩ፡፡ ባለፈው 3 ዓመት ሲሰራ የቆየው ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገቡ ሴት ተማሪዎች ከፍተኛ ችግር ስለነበረባቸው እነሱን መርዳት ነበር። ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከገቡት መካከል 70 በመቶ ትምህርት የሚያቋርጡት ሴቶች ነበሩ፡፡
በት/ቤቶቹ አካባቢ ከፆታ ትንኮሳ አልፎ ከባህል ያፈነገጡ አስነዋሪ ተግባራት ይፈፀሙ ነበር። ድርጅቱ ችግሮቹ ከምን እንደመጡ ለማወቅ ባደረገው ጥናት ሦስት ችግሮች ለይቷል፡፡ አንደኛው ችግር ለተመደቡበት አካባቢ አዲስ መሆን፣ የግንዛቤ ማነስና ከቤተሰብ ቁጥጥር ነፃ መሆን ነበር፡፡
ሁለተኛው የገንዘብ ችግር ነው፡፡ ብዙቹ ሴት ተማሪዎች ከገጠር የመጡ የአርሶ አደሩ ልጆች ስለሆኑ ከፍተኛ የገንዘብ ችግር ነበረባቸው፡፡ ለደብተር መግዣ እንኳ ይቸግራቸው ነበር፡፡ አገር በቀል በመሆናቸው የሁሉንም ሴቶች ችግር መቅረፍ ባይችሉም፣ ከአገር ውስጥ ባገኙት 10 ሚሊዮን ብር ለ1000 ሴት ተማሪዎች ትምህርታቸውን እስኪጨርሱ በየወሩ 200 ብር እየሰጡ እያስተማሩ እንደሆነ አቶ ያሬድ ገልጿል፡፡  ስለዚህ ሴት ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ከመግባታቸው በፊት መስከረም 5 ቀን በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ስኬታማ የሆኑ ሴት ተማሪዎች ላለፈው 3 ዓመት ተሞክሯቸውን እንዲያካፍሉ አድርገናል ብሏል፡፡ ይህን የልምድ ልውውጥ ያደረጉት በአዲስ አበባ፣ በድሬዳዋና በሐረሪ ሲሆን በአዲስ አበባ ብቻ 27 ሺህ ሴት ተማሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የሴቶች ችግር ውስብስብ ስለሆነ ለብቻው በማውጣት፣ ጥቅምት 5 ቀን 2007 ቀዳማይ እመቤት ሮማን ተስፋዬ በተገኙበት “ዘር ኢትዮጵያ” የተባለ ድርጅት ማቋቋማቸውን አቶ ያሬድ ግርማ ተናግሯል፡፡    

Saturday, 13 June 2015 14:56

ልጅቷ የምን ተማሪ ነች?

       እግር ጥሎኝ ምሳ ልበላ አዲስ አበባ ውስጥ ወደሚገኝ ወደ አንድ ፋስት ፉድ ቤት ጎራ አልኩኝ። በረንዳው ላይ ልቀመጥ ፈለግሁኝ፡፡ ይሁንና ከአንድ አነስተኛ ጠረጴዛና አራት ኩርሲዎች በስተቀር ማስተናገድ የማትችለዋ በረንዳ በደንበኞች ተይዛለች፡፡ አማራጭ አልነበረኝምና ወደ ውስጥ ገባሀኝ፡፡
እየገባሁ ግን እንደልማዴ ሰዎቹን ገርመም አደረግኋቸው፡፡ ሁለት ወንዶችና አንዲት ሴት፡፡ ሕጻን ልጅም ይዘዋል፡፡ ዓይኔ ሴቷ ላይ ትንሽ ቆየ። ቀይ፣ ነጥብ እንኳን የሌለው ጥርት ያለ ፊት፡፡ ያለ ሊፕስቲክ እንዲሁ በተፈጥሮ የቀላ ቀጭን ከንፈር። 17-18-19 ቢሆናት ነው፡፡ ከኩርሲዎቹ በአንዱ ለይ ተቀምጣ፣ ግድግዳውን በመደገፍ፣ አንደኛውን እግሯን ማዶ ካለው የበረንዳው አጥር ላይ እንደ መስቀል አድርጋለች፡፡ ምቾት ፍለጋ እንጂ የቅምጥል አይደለም፡፡ “መለሎ መሆን አለባት፡፡ በዚያ ላይ የደረቷ ሙላት!” ስል ተደመምኩኝ፡፡  
ቤቱ ውስጥ የተወሰኑ ሰዎች አሉ፡፡ ልብ አላልኳቸውም፡፡ ፈጣኑ አስተናጋጅ ገና ከመቀመጤ ሜኑ ይዞ መጣ፡፡ ሜኑውን ማየት ሳያስፈልገኝ “ቺዝ በርገር፣” አልኩኝ፡፡
“የሚሄድ ነው ወይስ…” ጠየቀኝ ጎንበስ ለማለት እየሞከረ፡፡
“አይ፣ እዚሁ የሚበላ፣” ብዬ ሞባይሌን አወጣሁኝና ፌስ ቡክ ከፈትኩኝ፡፡ ምንም አዲስ ነገር የለም፡፡ “አክቲቭ ፍሬንድስ” ላይ ተጫንኩኝ። የተለመዱ ሰዎች እንደተጣዱ ናቸው፡፡ ትቼ ወጣሁኝ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ለምን ፌስ ቡክ ውስጥ ዘልዬ እንደምገባ አላውቅም፡፡ “ምን ለማግኘት? ምን ለመጠቀም? በከንቱ ጊዜና ገንዘቤን በ 3ጅብ ለማስበላት?! እንድያው ምን ባደርግ ይሻለኛል?”
ድንገተኛ ዝናብ ካዘዝኩት ምግብ ጋር እኩል መጣ፡፡ “እንኳንም ውስጥ ገባሁኝ፡፡” በረንዳው ላይ የነበሩ ሰዎች ፒዛቸውን እንደያዙ ገቡና ከፊት ለፊቴ ያለውን አነስተኛ ጠረጴዛ ከበው ሰፈሩ፡፡ ልጅቷና አንደኛው ሰውዬ ጀርባቸውን ሰጥተዉኝ ተቀመጡ። ያኛው ሰውዬ ህጻኗን እቅፍ አድርጓት ከፊት ለፊት ለፊታቸው ተቀመጠ፡፡ አባቷ ሳይሆን አይቀርም፡፡ በጣም ይመሳሰላሉ፡፡
“ይሄኛውስ ሰውዬ ለዚህችኛዋ ቆንጆ ምኗ ይሆን?” ስል አሰብኩኝ፡፡ “መቼም ጓደኛዋ አይሆንም፤ ምክንያቱም ሰፊ የእድሜ ልዩነት ይታየኛል፡፡ የሱ ቢያንስ የሷ ሲባዛ ሁለት ሲደመር አንድ ይሆናል፡፡ … እንዴ፣ እኔ ምን አገባኝ…? ለምን ባሏ አይሆንም? …. ደግሞስ ፍቅርን ዕድሜ  ይወስናል ያለው ማን ነው? ጀኒፈር ሎፔዝ በ42 ዓመቷ የ18 ዓመት ወጣት “ጠብሳ” አልነበረም እንዴ? እኛስ ጎረቤት ጋሽ አህመድ አዲሷን ሚስታቸውን በ41 ዓመት ይበልጧት የለምን? ማን ናቸው ባላምባራስ….” እያልኩኝ ነገሩንና በርገሩን አንድ ላይ ሳላምጥ ጎርነን ያለ ድምፅ ከሃሳቤ አባነነኝ፡፡
“አስራ ሁለተኛ ክፍል’ኮ ነች፤ አታውቅም እንዴ? ኢንትራንስ ተፈታኝ ነች፣” ልጅቷ አጠገብ ያለው ሰውዬ ነበር፡፡
“አስራ ሁለተኛ? ከመቼው? እኔኮ ዘጠነኛ ወይ አስረኛ መስላኝ ነበር፣” አለ የህጻኗ አባት፡፡
“ምን የዘመኑ ልጆች እንደሆኑ ይገርማሉ፡፡ ገና ትምህርት ቤት ከመግባታቸው ሚኒስትሪ ደርሰው ታያለህ፡፡ ያ ሲገርምህ ድንገት ይጠፉብሃል፡፡ “የት ሄደው ነው?” ስትል ዩኒቨርሲት ገቡ ትባላለህ፡፡”
“በእውነት እኔ ኢንትራንስ ተፈታኝ ትሆናለች ብዬ አልገመትኩም ነበር፡፡”
“እንዴት ነው ግን ጥናት?” አለ አጠገቧ ያለው ሰውዬ ወደ ልጅቷ ዞሮ፡፡
ልጅቷ ሾል ያለውን የፒዛውን ጫፍ በትንሹ ገመጥ አድርጋ ትከሻዋን ከፍ ዝቅ አደረገች፡፡
“እንዴ?!” አለ ሰውዬው፡፡ “ፒዛ የተጋበዝሽው’ኮ ሳይኮሎጂካሊ ለፈተናው ዝግጁ እንድትሆኚ ነው፡፡ ደርሷል’ኮ”
ፈገግ አልኩኝ፤ በሆዴ፡፡ እርግጠኛ ነኝ ዘመዷ መሆን አለበት፡፡ አቀማመጣቸውና አነጋገሩ እንደዚያ ዓይነት ፍንጭ ይሰጣል…፡፡
“ተናገሪ እንጂ… እያጠናሽ ነው?” አላት፡፡
የህፃኗ አባት ልጁን ሚሪንዳ በጠርሙስ እያስጎነጫት ተራ በተራ ያያቸዋል፡፡
“እንዴ አዋ… እያጠናሁ ነው” አለች፡፡ ለስለስ ያለ ድምጽ አላት፡፡
 “እንደዚያ ከሆነ እስቲ ጥያቄ ልጠይቅሽ” አለና ማሰብ ጀመረ፡፡
“ኢንትራንሱ ተጀመረ” አልኩኝ ጥያቄው እንዳያመልጠኝ ማኘኬን ቆም አደረግሁኝ፡፡ ምን ዓይነት ጥያቄ ይሆን?
“እ… የአድዋ ጦርነት መቼ ተካሄደ?”
አሃ፤ የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪ መሆን አለባት፡፡ ወደ ልጅቷ ዞርኩኝ፡፡ ጀርባዋን ሰጥታኝ ስለተቀመጠች ፊቷን ማንበብ አልቻልኩም፡፡ ግን ልጅቷ ከኋላም ቆንጆ ነች፡፡ ከወገቧ ቀጠን ብላ ከመቀመጫዋ ሞላ ብላለች፡፡ “ናኑ ናኑ ነዬ” ትዝ አለኝ፡፡
ትንሽ አሰብ ካደረገች በኋላ፣ “1984” አለች፡፡
“እህ…?!!” የሚል የስቅታና የድንጋጤ ዓይነት ድምጽ ሰማሁኝ፡፡ ሰው ቤተ መጻህፍት ውስጥ ሆኖ ድንገት ሳያስበው ከኋላው በቀዝቃዛ ሹል ነገር ወጋ ቢደረግ የሚያወጣው ዓይነት ድምጽ ነው፡፡
አብሯቸው ያለው ሰውዬ ድንገት አገጩን ጣለና አፉ ውስጥ ያለው ምግብ ታየኝ፡፡ ዓይኖቹ ወጣ ወጣ ብለው ልጅቱ ላይ ተተክለዋል፡፡
ማን ነው ግን ያን ድምጽ ያወጣዉ? እኔ ነኝ እንዴ? ማለቴ ሰው ምግብ ሲውጥ ቢደነግጥ፣ እንደዚያ ዓይነት ድምጽ ሊያወጣ ይችላል? በሃፍረት ዙሪያዬን ቃኘት አደረግሁኝ፡፡ ዞሮ የሚያየኝ የለም። ተመስጌን!
“አስራ-ዘጠኝ-ሰማኒያ-አራት?” አላት ዘመዷ እያንዳንዷን ቃል ረገጥ እያደረገ፡፡
ልጅቷ ዝም አለች፡፡
ወዲያው የሆነ አጋጣሚ ትዝ አለኝ፡፡ ለአንድ ከዩኒቨርሲቲ ለተመረቀ ሰው ከጠቅላላ ዕውቀት በመነሳት ስለ ሶላር ሲስተምና ፕላኔቶች በፀሐይ ዙሪያ ስለሚያደርጉት ዑደት ገለጻ እያደረግኩኝ ሳለ የአንደኛዋ ፕላኔት ስም ጠፋብኝ፡፡ “ማን ነበረች…? ማን ነበረች…? ማታ ማታ እኮ ፀሐይ እንደጠለቀች ሰማዩ ላይ ጎልታ የምታበራዋ ኮከብ ነች፡፡ እንዴ…” እያልኩኝ ሳስብ ሳሰላስል ሰውየው ሊያስታውሰኝ ፈልጎ “ኦዞን?” አለኝ፡፡
ይህችኛዋ ልጅ የባሰች ናት፡፡ አድዋ የተካሄደው አስራ ዘጠኝ ሰማኒያ አራት ነው ትበል?
“አድዋ፣ አስራ-ዘጠኝ-ሰማኒያ-አራት?” አለ ዘመዷ እንደገና፡፡
“አዋ፣” አለች ልጅቱ፡፡ “እንደዚያ መሰለኝ፡፡”
አይ… በቃ ይህቺ ልጅ በርግጠኝነት የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪ አይደለችም፡፡ ብትሆን ኖሮ ሂስትሪ ትምህርት ላይ ስለምትማር  ሰማኒያ ስምንት ዓመት ቀንሳ አትናገርም ነበር፡፡  የፈረንጆቹን የዓመት አቆጣጠር ከተጠቀመች ማለቴ ነው፡፡
“እንዴ አስራ ዘጠኝ ሰማኒያ አራትማ አይደለም።” አላት ዘመዷ፡፡
ልጅቷ ትከሻዋን ከፍ ዝቅ አደረገች፣ በግድ-የለሽነት፡፡
ቢጨንቀው ነው መሰለኝ የህፃኗ አባት “በኢትዮጵያ ነው በፈረንጅ?” ብሎ ጠየቃት፡፡ ሳቄን ያዝ አደረግሁት፡፡
አፏን በሶፍት እየጠረገች፣ “በኢትዮጵያ” አለች፡፡
አሁን እንኳን አልቻልኩም፡፡ የያዝኩትን አስቀምጬ ከት ብዬ ሳቅሁኝ፣ ምንም እንኳን በሆዴ ቢሆንም፡፡
“በኢትዮጵያ 1984 ማለት’ኮ ትላንት ነው፤ ምናልባት አንች ተወልደሽ ሊሆን ይችላል” አላት የህጻኗ አባት፡፡
ልጅቷ መልስ ሳትሰጥ ህጻኗን ከፒዛው እየቆነጠረች ማጉረስ ጀመረች፡፡
“የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ ትሆናለች፤ ለምን በታሪክ ጥያቄ ያስጨንቋታል?” ስል አሰብኩኝ፡፡
“ቆይ ከ1984 ወዲህ ስንት ዓመት ነው?” ብሎ ጠየቀ የህጻኗ አባት፡፡ እስካሁን ግርምቱ አልለቀቀውም፡፡ ግን አገጩ ወደ ትክክለኛው ቦታ ተመልሷል፡፡ እሱ ይሆን እንዴ የቅድሙን ድምፅ ያወጣው?
ጎሽ! እንደዚህ ሂሳብ ነክ ጥያቄ ይሻላል፣ ከትምህርቷ ጋር የሚሄድ”… ስል አሰብኩኝ። “ግን የአድዋን ጦርነት ዓመት እቅጩን እንኳን ባያውቁ፣ እንዲያው ተቀራራቢ ግምት ለመስጠት የግድ የሕብረተሰብ ሳይንስ ወይም የታሪክ ተማሪ መሆን ያስፈልጋል እንዴ? በየዓመቱ የካቲት 23 መታሰቢያው ይከበር የለ?”
ልጅቷ ከ1984 ወዲህ ስንት ዓመት እንደተቆጠረ ለመመለስ አይኗን ጣሪያው ላይ ተከለች፡፡ እኔም አይኖቿን ተከትዬ ጣሪያው ላይ አንጋጠጥኩኝ፡፡ ልክ እንደ ግድግዳው ሁሉ ጣሪያውም በበርገርና በፒዛ ስዕሎች አሸብርቋል፡፡ የትኛውን መምረጥ እንዳለባት የተቸገረች ይመስል አይኖቿን ከአንደኛው ስዕል ወደ ሌላኛው ታንከባችልላለች፡፡
ጨነቀኝ፡፡ መቶ ዓመት እንዳትል ብዬ ፈራሁኝ፡፡
በመጨረሻም ዓይኖቿን ከጣሪያው ላይ አንስታ ጠያቂዋ ላይ አኖረች፡፡ አውጥታ አውርዳ ያገኘችውን መልስ ነገረችው፤ “ከ1984 ወዲህ… እኔ እንጃ ፡፡ ስንት ዓመት ነው?”
“የባሰው መጣ!! ቆይ ይህቺ ልጅ የምን ተማሪ ናት? ታሪክ ካላወቀች የህብረተሰብ ሳይንስ ተማሪ ላትሆን ትችላለች፡፡ ሂሳብ ላይ ዜሮ ከሆነች የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ አይደለችም ማለት ነው፤ ምክንያቱም እንዲህ ዓይነት የሂሳብ ችሎታ ይዞ ሳይንስ የሚደፍር የለም፡፡”
“አንቺ ልጅ በዚህ ሁኔታ ነው ኢንትራንስ የምትፈተኚው? ማጥናት’ኮ አለብሽ!” አላት ዘመዷ፡፡
“እያጠናሁ ነኝ፡፡”
“እያጠናሽ ነው?” አለ በፌዝ ቅላፄ፡፡ “እንደዚያ ከሆነ እሽ ሌላ ጥያቄ ልጠይቅሽ፡፡ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከመቼ እስከ መቼ ተካሄደ?”
“ይሄ ደግሞ ምኑ ጦረኛ ነው?” አልኩኝ ለራሴ፡፡ “ሌላ ጥያቄ የለውም?”
ልጅቷ እንዳልሰማች ህጻኗን ማጫወት ጀመረች።
“መልሽ እንጂ”
“እያሰብኩ ነው”
“ይሄ’ኮ ማሰብ የሚያስፈልገው አይደለም። በአንዴ ተረክ የሚደረግ ነው፡፡” አላት ዘመዷ እንዳያሳፍራት ሳቅ እያለ፡፡
“በ1911 ነው የተጀመረው፣” መለሰች፡፡
“አይደለም፡፡ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተካሄደው፣ ትሰሚያለሽ፣ ከ 1939 እስከ 1945 ነው።” አላት ቃላቶቹን ረገጥ እያደረገ፡፡ ልጅቷ ዝም አለች፡፡ “እሺ ለጦርነቱ መጀመር ዋናው ምክንያት ምንድነው፣ አጣዳፊውስ ምክንያት ምንድነው?”
ዝም፡፡
“ማን ተገድሎ ነው ጦርነቱ የተጀመረው?”
ዝም፡፡
ምናልባት እዚህ ጋ ሰውዬው የኦስትሪያውን አልጋ ወራሽ የፍራንሲስ ፈርድናንድን መገደል አስቦ ከሆነ ተሳስቷል ማለት ነው፣ ምክንያቱም ይሄ ለአንደኛው የዓለም ጦርነት መለኮስ አጣዳፊው ምክንያት ነው እንጂ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጋር አይገናኝም፡፡
“እሺ ዘመነ መሳፍንት ከስንት ዓመተ ምህረት እስከ ስንት ዓመተ ምህረት ተካሄደ?”
ዝም፡፡
“እሺ ዘመነ መሳፍንትን ያስቆመው ንጉስ ማን ነው?” እነዚህንና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች ከኢትዮጵያና ከዓለም ታሪክ እያቀላቀለ ጠየቃት። ልጅቷ ግን አንዱንም እንኳን ስትመልስ አልሰማሁም። ሰውዬው ግን የተወሰነ የታሪክ ዕውቀት እንዳለው ተገንዝቤአለሁ፡፡
“አንቺ ልጅ ዋ! ዩኒቨርሲቲ ሳትገቢ ትቀሪና!”
“እንዴ! እገባለሁ፡፡ ኮራ ብዬ ነው ለዛውም”
እስከ ጆሮዎቼ ድረስ ፈገግ አልኩኝ፡፡ ከሕፃኗ አባት ጋር ዓይን ለዓይን ተጋጨን፡፡ ፈገግ አለ እሱም። አፍሬ ዓይኔን ጣሪያው ላይ ተከልኩኝ፡፡ ወዲያው ሃሳብ ይዞኝ ሄደ፡፡ ይህቺ ልጅ አሁን ምንና እንዴት ተምራ ነው እስከዚህ የደረሰችው? የትምህርት ቤቷንና ሀገር-አቀፍ ፈተናዎችን እንዴት አልፋ ነው ዩኒቨርሲቲ ለመግባት አንድ ሐሙስ የቀራት? ምንስ ብትተማመን ነው ዩኒቨርሲቲ እንደምትገባ እርግጠኛ ሆና የምትናገረው?
በርግጥ በእነዚህ ጥያቄዎች ብቻ ስለ ልጅቷ ዕውቀትና ትምህርት ጠለቅ ያለ ግንዛቤ ማግኘት ባይቻልም፣ መሠረታዊ የሒሳብ ዕውቀት ከሌላት፣ ስለ ወሳኝ የዓለምና የሀገራችን ክስተቶች መሠረታዊ ግንዛቤ ከሌላት፣ ሌላ ምን ማለት ይቻላል?
“ወንድም ይቅርታ… ልወጣ ስለሆነ ሒሳብ ትሰጠኛለህ?... ካላስቸገርኩህ?”
ከሀሳቤ ተመለስኩኝ፡፡ “ኧረ ችግር የለውም፡፡”
ሰዎቹ የሉም፡፡ ዞር ብዬ ወደ ውጭ አየሁኝ፤ ዝናቡም ቆሟል፡፡ እንዴ መቼ ወጡ?

Published in ህብረተሰብ
Saturday, 13 June 2015 14:54

‹‹የሰው ዘር መገኛ››

ዳርዊን እና ወንጌል ሊታረቁ ይችላሉን?

የዩኒቨርስቲ ተማሪ ሳለሁ፤ ከጓደኞቼ ጋር ወደ አንድ መምህራችን ቢሮ ሄድን፡፡ የሄድንበትን ጉዳይ አሁን አላስታውሰውም፡፡ ይሁንና በዚያ አጋጣሚ መምህራችን ያለውን አንድ ነገር እስከ ዛሬ አስታውሰዋለሁ፡፡ ወደ እርሱ ቢሮ የሄድንበትን የትምህርት ጉዳይ ተነጋግረን ከጨረስን በኋላ፤ መምህራችን የእግዚአብሔርን ህልውና የሚጠይቅ ሐሳብ ያለው አንድ ግጥም አነበበልን፡፡ ከዚያም ከመሀላችን አንዱ፤ ‹‹ግን አንተ በእግዚአብሔር አታምንም›› ሲል ጠየቀው፡፡ መምህራችን ፈጠን ብሎ ‹‹እኔ አላምንም›› አለ፡፡
ጨዋታው ቀጠለ፡፡ ወሬያችን እንደ ፈሰሰ ውሃ የራሱን መንገድ እየፈለገ ሄዶ፤ መምህራችን በኢህአፓ ዘመን ያጋጠመውን ችግር ከሚያወራበት ቦታ ደረስን፡፡ ሲያወራ ቆይቶ፤ ‹‹በስመ አብ [በስማም] ያኔ የተፈጠረው ችግር›› ብሎ ወሬውን ሊቀጥል ሲል፤ ከመሐላችን አንዱ በጣም ሳቀ፡፡
‹‹ምነው?›› አለ መምህራችን፡፡
‹‹አሁን እኮ በስማም አልክ››
‹‹አይ እሱ ልማድ ነው›› በማለት፤ እንደ ዋዛ መልሶለት ጨዋታውን ቀጠለ፡፡
ከዚህ ጋር አብሮ ሊነሳ የሚገባው ሌላ ነገር አለ። ሐይማኖተኛ መሆኑ በግልፅ የሚታወቅ የኮሌጅ፣ የዩኒቨርስቲ ወይም የሁለተኛ ደረጃ መምህር፤ ያለ አንዳች ሰቀቀን ‹‹የአዝጋሚ ለውጥ›› ቲዮሪን ሊያስተምር ይችላል። ‹‹የእሱ እንኳን እንጀራ ሆኖበት ነው›› ብለን እንለፈው። መምህሩም የዳርዊንን ቲዮሪ እንደማይቀበለው ገልፆ ሊያስተምር የሚችል ይመስለኛል፡፡ ሆኖም በትምህርቱ አሰጣጥ ላይ የእርሱ እምነት መንፀባረቅ የለበትም። ስለዚህ ‹‹ፖለቲካዊ ትክክለኝት›› ይህን እንዲያደርግ ያስገድደዋል፡፡ የእርሱ ዕዳው ገብስ ነው፡፡
ደግሞ ሌላ ነገር ልጨምር፡፡ አንድ ጓደኛዬ ስድስተኛ ክፍል ሳለች ያጋጠማትን ነገር ነገረችኝ፡፡ ‹‹ለኅብረተሰብ ፈተና ስዘጋጅ እያለሁ፤ ጓደኛዬ መጥታ፤
‹አምና የመጣ አንድ ጥያቄ ልንገርሽ› አለችኝ፡፡
‹ምንድነው?› አልኳት፡፡
‹ሰው የተፈጠረው…………..ሀ). ከክሮግማኖን ለ). ከአዳም እና ሔዋን ሐ). በአዝጋሚ ለውጥ ሂደት መ). መልሱ የለም› ብላ ጥያቄውን ስትነግረኝ፤ በልቤ አንድ ነገር አሰብኩ፡፡ ከአስሩ ጥያቄ መልሳቸውን በትክክል የማውቃቸውን ቆጥሬ ከአምስት በላይ ከሆኑ ‹አዳም እና ሔዋን› ብዬ እመልሳለሁ፡፡ ከአምስት በታች ከሆኑ …….› ብዬ አሰብኩ፡፡ ግን እስከ ዛሬ ድረስ እንደዚያ ማሰቤ ይቆጨኛል፡፡ አዝናለሁ›› አለች  እንደ መተከዝ ብላ። የማዘኗ እና የመቆጨቷ ነገር አልገባኝም፡፡ ስለዚህ፤  ‹‹ለምንድነው የሚቆጭሽ? ምንድነው የሚያሳዝንሽ?›› አልኳት፡፡
‹‹አሁን ለአንተ ስነግርህም እንደ ንስሐ በማሰብ ነው›› አለችኝ፡፡
ነገር የማጋነን ችግር ውስጥ የገባች መሰለኝ፡፡ በመጨረሻም፤ ‹‹ያን ጊዜ፤ ለአንድ ማርክ ብዬ እንደዚያ ማሰቤ ያሳዝነኛል›› አለችኝ፡፡ እንዳሰብኩት፤ ነገር የማጋነን ጉዳይ አልነበረም፡፡ ከምሯ ነው፡፡ ከልብ ተቀበልኳት፡፡
ይህች ጓደኛዬ እንደ መምሬ በዝንጋኤ አልተኛችም፡፡ ጥያቄው ሲቀርብላት፤ ‹‹በኅብረተሰብ ሳይንስ የተማርነው ምንድነው?›› በሚል ልማዳዊ ተግባር መልስ ለመስጠት አልተጣደፈችም፡፡ ነገሩን በልማዳዊ አባባል አለባብሳ አላለፈችውም፡፡ ቆም ብላ አስባለች፡፡ የቻርልስ ዳርዊንን የአዝጋሚ ለውጥ ሐልዮት አትቀበልም፡፡ ያን ጊዜ፤ ‹‹ትምህርታዊ ትክክለኝነት›› ወይም ማርክን በማሰብ፤ ጨርሶ የማታምንበትን ነገር እንደ መልስ ለማቅረብ ማሰቧ እንኳን ዘግንኗታል፡፡ የአስተማሪው ብዙ ምርጫ ያለው አይመስለኝም፡፡ ተማሪውም ሌላ አማራጭ የለውም፡፡ ግን ነገሩን እንደ’ኔ መምህር ተራ የቋንቋ ልማድ አድርጎ ከማየት ወይም ከዝንጋኤ መራቅ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ አንዳንድ ኢ-አማኒ መሆናቸውን የሚገልፁ፤ እንደ ማክሲም ጎርኪ ያሉ ፀሐፊዎችም ‹‹መንፈሳዊ›› ወይም ‹‹ነፍስ›› የሚል ቃል ሲጠቀሙ፤ እንደ ዘይቤ ወስደውት ይሆናል፡፡ ለምሣሌ ጎርኪ ‹‹On Literature›› በሚል መፅሐፉ፤ ‹‹እኔ ‹ነፍስ› የሚለውን ቃል የምጠቀምበት እንደ ዘይቤ ነው›› ማለቱን አስታውሳለሁ፡፡   
እንደ ተማሪ ‹‹ትምህርታዊ ትክክለኛነት፤ እንደ መምህር ‹‹ፖለቲካዊ ትክክለኛነት›› እያስገደዳቸው የዳርዊንን የአዝጋሚ ለውጥ ሐልዮት የመቀበል ዕዳ ሊወድቅባቸው ይችላል፡፡ እንዲህ ዓይነት ችግር የሌለባቸው፤ እንዲያውም ህይወታቸው እና በግልፅ የሚታየው እምነታቸው ከዳርዊን ጋር የሚጋጭ ሆኖ ሳለ፤ ‹‹ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ ነች›› ሲሉ የሚናገሩ አንዳንድ የሐይማኖት አባቶችን ማየት ግን ግራ ያጋባል፡፡ እነዚህ አባቶች፤ ‹‹ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ ነች›› ሲሉ በተደጋጋሚ እሰማለሁ፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች በመገኛኛ ብዙሃን የቀረቡ፤ አንዳንድ የሐይማኖት ሰዎች፤ ‹‹ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ ነች›› ሲሉ እናንተም ሰምታችሁ ይሆናል፡፡ ታዲያ እነዚህ አባቶች፤ ‹‹ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ›› ሲሉ ምን ማለታቸው ይሆን? ‹‹ኢትዮጵያ አዳም የተፈጠረባት ሐገር ነች›› ማለታቸው አልመሰለኝም፡፡   
ለምሣሌ፤ የዳርዊንን የአዝጋሚ ለውጥ የማይቀበል አንድ የባህል ወይም የቱሪዝም ተቋም የሥራ ኃላፊ፤ ‹‹ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ›› ቢል፤ ነገሩ ‹‹ከኢኮኖሚያዊ ትክክለኝነት›› ጋር መያያዙ ግልፅ ነው፡፡ ከዚያ የተለየ ነገር እንዲልም አይጠበቅም፡፡ የሐይማኖት አባቶች ጉዳይ ግን ግራ ያጋባል፡፡ የዳርዊን ሐልዮት እና የመፅሐፍ ቅዱስ ቃል አይጋጩባቸውም ማለት ነው?
 አንዳንድ ሰዎች፤ ‹‹ሳይንስ እንደ ድሮው ሐይማኖትን የሚፃረር ሆኖ አይታይም፡፡ ይልቅስ፤ የሳይንስ አንዳንድ ግኝቶች ሐይማኖትን የሚያግዙ ሆነዋል›› በማለት ይገልፃሉ፡፡ ኬሊ ቤሴክ (Kelly Besecke) የተባለ የማህበራዊ ሳይንስ ምሁር ባቀረበው አንድ ጥናታዊ ፅሁፍ፤ በምዕራቡ ዓለም፤ ‹‹ሳይንስ እና ሐይማኖት ወይም እምነት እና አመክንዮ አይጋጩም›› የሚል እምነት ያላቸው ሰዎች መኖራቸውንም ይጠቅሳል፡፡ በዚሁ ጥናታዊ ፅሑፍ፤ ሐንክ ሃኔግራፍ (Hank Hanegraaff) የተባለ ታዋቂ አሜሪካዊ ፀሐፊ፤ ‹‹Adam and Eve: Fact or Fiction›› በሚል ርዕስ አንድ መጣጥፍ መፃፉን የሚጠቅሰው ኬሊ ቤሴክ (Kelly Besecke) በዚሁ መጣጥፍ መነሻ፤ የሚከተል ጥያቄ እና መልስ መስፈሩን ይናገራል፡፡
ጥያቄ፤ መፅሐፍ ቅዱስ መንፈሳዊ ይዘት እንዳለው የሚያምን አንድ ጓደኛዬ፤ በቅዱስ መፅሐፍ የተጠቀሰው የአዳም እና የሔዋን ታሪክ፤ እንዲሁም ውድቀታቸው በቀጥታ ሊወሰድ አይገባውም ብሎ ያምናል፡፡ ታዲያ የዚህ ጓደኛዬን ሐሳብ የሚደግፍ ቃል በመፅሃፍ አለ?
መልስ፤ በፍፁም! የአዳም እና የሔዋን ታሪክን እንዲሁም ነገረ-ውድቀት እና ሞታቸውን እንደ ዘይቤአዊ አገላፅ መውሰድ (Figurative allegory አድርጎ)፤ ጠቅላላ የመፅሐፍ ቅዱስን ቃል በከፋ መልክ የሚፃረር አስተያየት ነው፡፡
ሐንክ ሃኔግራፍ፤ በአሜሪካውያን ዘንድ ሰፊ ዝና ያለው ሰባኪ ነው፡፡ አሜሪካውያን ‹‹Bible Answer Man›› እያሉ ይጠሩታል፡፡ በየዕለቱ እንዲህ ያሉ ጥያቄዎች እየቀረቡለት ምላሽ ይሰጣል፡፡ የሚሰጠው ምላሽ፤ በመላ አሜሪካ በሚገኙ ከመቶ የሚበልጡ የሬዲዮ ጣቢያዎች ይተላለፋል፡፡
ሐንክ ሐኔግራፍ፤ ከመፅሐፍ ቅዱስ የተለያዩ ጥቅሶችን እየወሰደ፤ የአዳም እና የሔዋንን ታሪክ ሥነ መለኮታዊ ፋይዳ እና ታሪካዊ ትክክለኛነቱን ካስረዳ በኋላ፤ ‹‹የአዳም እና የሔዋንን ታሪክ ቃል በቃል መቀበል እና እውነተኛነቱን ማረጋገጥ ለአንድ ክርስቲያን በጣም አስፈላጊ መሆኑን አስረዳ፡፡ እንዲህም አለ፤
‹‹አየህ፤ በአዳም እና ሔዋን ታሪክ ላይ የሆነ ጥርጣሬ ካሳደርክ፤ በመፅሐፍ ቅዱስ መንፈሳዊ ይዘት እና የህይወት መመሪያ ቃል መሆኑ ላይ ጥያቄ ማንሳት ይኖርብሃል። በሰው ልጅ የሐጥያት ባርያ መሆን፣ በእግዚአብሔር ፀጋ ድኅነት በማግኘቱ ወዘተ ላይ ጥያቄ ማንሳትህ አይቀርም። በእነዚህ ጉዳዮች ጥያቄ ካነሳህ ክርስትያንነትህ ያበቃለታል፡፡››
የ‹‹ኢ-አማኒያን›› መፅሔት አዘጋጅ፤ እንዲሁም የአሜሪካ ኢ-አማንያን የፕሬስ ዳይሬክተር የሆነው ፍራንክ ዚንድለር፤ (Frank Zindler) በአንድ መጣጥፉ የሚከተለውን ይላል፤
‹‹ባዮሎጂ፤ በክርስትና እምነት ላይ ያመጣው ትልቅ አደጋ የአዝጋሚ ለውጥ ቲዮሪ ነው፡፡ ዛሬ አዳም እና ሔዋን በምድር ላይ ኖረው ያለፉ እውነተኛ ሰዎች አለመሆናቸውን አውቀናል፡፡ የክርስትና እምነት መሠረት የሆነው ታሪክ ፈራርሷል፡፡ እናም አዳም እና ሔዋን እውነተኛ ሰዎች ካልሆኑ፤ የመጀመሪያው ሐጢያት (original sin) የሚባል ነገር አይኖርም፡፡ የመጀመሪያው ሐጢያት የሚባል ነገር ከሌለ፤ ድኅነት አስፈላጊ አይሆንም፡፡ ድኅነት አስፈላጊ ካልሆነ፤ አዳኝ አያስፈልግም፡፡ አዳኝ የማያስፈልግ ከሆነ ኢየሱስ ምን ይሰራል፡፡ እንደኔ ሐሳብ የአዝጋሚ ለውጥ ቲዮሪ፤ የክርስትና እምነት መግነዝ ነው›› ሲል ጽፏል፡፡ በስመ አብ ማለት አሁን ነው፡፡
ሰባኪው ሐንክ ሐኔግራፍ በበኩሉ፤ የአዝጋሚ ለውጥ ሐልዮት ከክርስትና እምነት ጋር የሚጋጭ መሆኑን በመግለፅ፤ ለሬዲዮ አድማጮቹ ‹‹የቻርልስ ዳርዊንን ቲዮሪ እንዳትቀበሉ›› ሲል ጥሪ ያደርጋል፡፡ ለፍራንክ ዚንዲለር፤ ከአዳም እና ሔዋን ታሪክ ይልቅ ተቀባይነት ያለው ሳይንስ ነው፡፡ ታዲያ እነዚህ ተቃራኒ አቋም ያላቸው ሁለት ሰዎች፤ የሚጋሯቸው ሁለት ነጥቦች አሉ፡፡ አንደኛ፤ ሁለቱም ሰዎች፤ የዘፍጥረት ትረካ እና የአዝጋሚ ለውጥ ሐቲት የሚያጋጩ መሆናቸውን ያምናሉ፡፡ ሁለተኛ፤ ‹‹የሳይንስን (የአዝጋሚ ለውጥ) ትረካን መቀበል ክርስትናን መካድ ነው›› ይላሉ፡፡
ከፍ ሲል በጠቀስነው የኬሊ ቤሴክ (Kelly Besecke) ጥናታዊ ፅሑፍ እንደ ተጠቀሰው፤ የሐንክ ሐኔግራፍ እና ፍራን ዚንድለር የክርክር ሎጂክ ለብዙ አሜሪካውያን ፀነን ይልባቸው ይሆናል፡፡ ሆኖም፤ ሁለቱ ተከራካሪዎች ይስማሙባቸዋል ያልናቸው ሁለት ነጥቦች፤ የአሜሪካ የዕውቀት ማህደር ጥንታዊ ጓዝ ናቸው፡፡ የዘፍጥረት እና ‹‹የአዝጋሚ ለውጥ›› ክርክር የተለመደ የአሜሪካውያን ባህላዊ ጓዝ ነው፡፡
በዚህ የተነሳ፤ አንዳንድ የአሜሪካ ቤተክርስቲያናት፤ በተጠቀሱት ጉዳይ ላይ ያተኮሩ ሥልጠናዎችን ይሰጣሉ። ‹‹እምነት እና አመክንዮ›› (Faith and Reason) እንዲሁም፤ ‹‹እዩር መፅሐፍ ቅዱሳዊ ንባብ›› (Reading the Bible intelligently) የሚሉ ሥልጠናዎችን ለወጣቶች (ጎልማሶች) ይሰጣሉ፡፡ ኬሊ ቤሴክ (Kelly Besecke)፤ ‹‹በእነዚህ የትምህርት መስጫ ክፍሎች እግር ጥሎት የገባ ሰው፤ በእነዚህ ክፍል ውስጥ የሚሰማው ውይይት የሚከተለውን ይመስላል›› ይላል፡፡
አሊስተር፣ እኛ በአንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበሩ ሰዎች ወይም ወንጌላውያን በእዕምሯቸው ያብሰለስሉ የነበረው ጥያቄ ምን እንደሆነ ለማሰብ ሳንሞክር፤ መጽሐፍ ቅዱስ የእኛን ዘመን ጥያቄ እንዲመልስልን እንሻለን፡፡ ምሳሌ፤ ሊሆን የሚችለው ዘፍጥረትን በማንበብ ስለ አዝጋሚ ለውጥ ሂደት ለመረዳት መሞከራችን ነው፡፡ ሆኖም ዘፍጥረትን በፃፉት ሰዎች፤  አዕምሮ ውስጥ የሳይንስ ጥያቄ ይኸ አልነበረም፡፡ የአዝጋሚ ለውጥ ሂደት የሚያስጨንቃቸው ሰዎች አልነበሩም፡፡ የዘፍጥረት ዋና መልዕክት፤ ‹‹ከዚህ ከምናየው ዩኒቨርስ ጀርባ፤ እግዚአብሄር አለ›› የሚል ነው። እኔም ያለ አንዳች ጥርጥር ይህን አምናለሁ፡፡
ዳን፤ እኔ መፅሐፍ ቅዱስ፤ ሳይንሳዊ ጥያቄዎች አለመመለሱ አያስጨንቀኝም፡፡ ምክንያቱም፤ ሳይንስ የህይወትን ውስብስብ ጥያቄዎች ለመመለስ አይሞክርም፡፡ ያን ለማድረግም አይችልም፡፡
አሊስተር፤ አዎ፤ መፅሐፍ ቅዱስ፤ የሳይንስን ጥያቄ አይመልስም፡፡ ይህም እንደ እንከን ሊታይ አይችልም። መጽሐፍ ቅዱስ ከሳይንስ ክበብ ውጪ ያለ መሠረታዊ ጥያቄን ለመመለስ ነው የሚሞክረው፡፡ ሳይንስ፤ ዕውቀት የሚገኝበት አንድ ጎዳና ነው፡፡ አንድ የዕውቀት መንገድ ብቻ ነው፡፡
እኛ አሁን እያደረግን ያለነው፤ ለሳይንስ ጥያቄ መፅሐፍ ቅዱስ ምላሽ እንዲሰጠን መፈለግ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ፤ ለእንዲህ ዓይነት ዕውቀት መፍቻ ቁልፍ የለውም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን ፅፈው ያኖሩልን ሰዎች፤ እንደዚህ ያሉ ሳይንሳዊ ጥያቄዎች አልነበራቸውም፡፡ እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች፤ በሳይንሳዊ ትርጉም ሳይሆን፤ በ‹‹ሥነ-ግጥማዊ›› ትርጉም ለማየት መሞከር አለብን፡፡
የእነዚህ ሁለት ሰዎች ንግግር በሳይንስ እና በሐይማኖት መካከል እርቅ ማውረድ አይደለም፡፡ አንዱን ይዘው፤ አንዱን ለመጣል አይፈልጉም፡፡ የሁለቱ ሰዎች ንግግር፤ በሳይንስ እና በእምነት መካከል ግጭት መኖሩን የሚቀበል አስተሳሰብን የሚገዳደር አመለካከት ነው፡፡ ነገሩን በሳይንስ መንገድ ብቻ ለማየት የሚሞክሩ ሰዎች (literalist science)፤ እንዲሁም በሐይማኖት ብቻ ለማየት የሚጣጣሩ ወገኖች (literalist religion)፤ ካሉበት አንዲት መንደር ገብተው፤ ሦስተኛ መንገድ እየፈለጉ ያሉ ሰዎች ናቸው፡፡ አዲስ የጥበብ ጥያቄ ቀያሾች ናቸው፡፡ የማህበራዊ ሳይንስ ጠቢባን፤ እነዚህን ሰዎች ‹‹አገናዛቢ ሐይማኖታውያን›› (reflexive spiritualists) ይሏቸዋል፡፡
የሆነ ሆኖ፤ ቻርልስ ዳርዊን እና ወንጌል ሊታረቁ ይችላሉ? የሚል ጥያቄ አሁንም መልስ አላገኘም፡፡ አሁን በምዕራቡ ዓለም ያለው አዝማሚያ እንዲህ ያሉ አስተሳሰቦች እየተጠናከሩ መምጣታቸውን ነው፡፡ ታዋቂው የማህበራዊ ሳይንስ ምሁር ማክስ ዌበር፤‹‹ትምህርት ሲስፋፋ ሐይማኖት እየጫጫ እና እየተዳከመ  ይመጣል›› ይል ነበር፡፡ በተቃራኒው፤ ‹‹አሁን ያ ድምዳሜ ስህተት መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ ተቋማዊ ሐይማኖታዊነት እየተዳከመ ቢመጣም፤ ሰዎች ከሐይማኖት ርቀዋል የሚል ድምዳሜ መያዝ አይቻልም፡፡ ብዙ ሰዎች ወደ ቤተክርስቲያን ሲሄዱ አለማየታችን፤ ሊያታልለን አይገባም›› የሚሉ ጸሐፊዎችም አሉ፡፡ እንደ ምሳሌ፤ የ9/11 አደጋ በተከሰተ ጊዜ በርካታ አሜሪካውያን ወደ ቤተ እምነቶች መጉረፍ መጀመራቸውን የሚጠቅሱም አሉ፡፡ የምዕራቡ ዓለም እንደሚታሰበው ሴኩላሪዝም የተስፋፋበት አይደለም፡፡ የምዕራቡ ዓለም፤ ከሞት በኋላ ህይወት የለም የሚሉ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ፤ ከሞት በኋላ ያለውን ሁኔታ እግዚአብሔር ፈቅዶልኝ አይቼ ጎብኝቼ መጣሁ ብለው፤ የወዲያኛውን ዓለም በሚደንቅ ሁኔታ እየገለፁ የፃፉ ሰዎችም አሉ፡፡ ከእነዚህ ሰዎች አንዱ አማኑኤል ስዌደንቦርጅ ነው፡፡
አማኑኤል ስዌደንቦርጅ (Emanuel Swedenborg)፤ ‹‹ገነት እና ሲዖል›› (Heaven and Hell) የሚል መፅሐፍ አለው፡፡ መፅሐፉ ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመው በ1758 ዓ.ም ሲሆን፤ የተፃፈውም በላቲን ቋንቋ ነበር፡፡ በአሜሪካ፤ የመጀመሪያው የእንግሊዝኛ ትርጉም  የታተመው፤ በ1812 ዓ.ም ሲሆን፤ እኔ ያነበብኩት መጽሐፍ፤ በጆርጅ ኤፍ. ዶሌ የተተረጎመ የ1994 ዕትም ነው፡፡ አማኑኤል ስዌደንቦርጅ (Emanuel Swedenborg) ከፃፋቸው በርካታ መጽሐፍት እንደ ትልቅ ሥራ የሚቆጠረውም ‹‹ገነት እና ሲዖል›› (Heaven and Hell) ነው፡፡  በዚህ መጽሐፉ፤ ስዌደንቦርጅ በመንፈሳዊው አውራጃ ከሞት በኋላ ያለውን ህይወት ‹‹ገጠመኝ ወይም አየሁ›› ያለውን በዝርዝር ገልፆ ያስነብበናል፡፡ መጽሐፉ በጣም የተደራጀ ሐሳብ ያለው እና ሰማያዊ ኑሮን በዝርዝር የሚያትት ነው፡፡ ስዌደንቦርጅ፤ ስለ ዩኒቨርሳል ንግግር (universal speech)፤ ከሞት በኋላ ስላለው ነገር፤ ስለ ግብዝ እና ቅዱስ ፍቅር፤ ስለ መናፍስት ዓለም እና ስለሌሎች በርካታ ነገሮች በዚሁ መጽሀፍ ያጫውተናል፡፡ በገነት እና ሲኦል የተገለፀው ሐሳብ ለ200 ዓመታት ያክል ከፍተኛ ውዝግብ ፈጥሮ ነበር፡፡
‹‹ስዌደንቦርጅን፤ በዘመነ አመክንዮ (age of reason) የተፈጠረ፣ ድንቅ እና ወጥ ሀሳብ ያለው አሰላሳይ ነው›› በማለት የሚያደንቁት አሉ፡፡ መጽሐፉ ‹‹ከሞት በኋላ ምን ይገጥመን ይሆን?›› የሚል ሀሳብ ብዙ ለሚያሳስባቸው ሰዎች ትንሽ ፍንጭ የሚሰጥ ነው፡፡
በሰው ልጅ ህይወት ውስጥ አያዋዊ ነገሮች ይከሰታሉ፡፡ እጃችን፤ ግዙፍ ነገሮችን ዳሶ ይለያል፡፡ ዓይናችን ቀለም እና ቅርፅን ይለያል፡፡ የዕለት ተለት ህይወት ኑሮአችን አድማሱ ጠባብ ነው፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ ነፍሳችን ከፍ ካለ ኮረብታ ወጥታ ማህለቅት የለሽ እውነታን ለቅጽበት የምትመለከትበት አጋጣሚ አለ፡፡ አያዋዊው ነገር ይህ ነው። በሌላ አገላለፅ፤ በጣም ውስን የዕድሜ ገደብ ያለው የሰው ልጅ፤ ዘላለምን ለመመልከት መቻሉ አያዋዊ ያደርገዋል፡፡ በዘላለም መስኮት ብቅ ብለው በቅጽበት እውነታን ለማየት የሚችሉ ፃድቃን ወይም ገጣሚዎች ወይም ፈላስፎች ብቻ አይደሉም፡፡ ሁላችንም በሆነ የደስታ እና ዘና የማለት ስሜት ውስጥ ስንሆን በጨረፍታ ነገሩን ለማየት የሚያስችል ዕድል ሊገጥመን ይችላል፡፡ ከእውኑ በላይ እውን የሆነ እና ከዘወትራዊ ኑሮ የላቀ የእይታ መስኮት አለ፡፡
በእርግጥ፤ ለኛ እውናዊ ዓለም ማለት በዙሪያችን የከበበን ግዘፋዊ አካባቢ ነው፡፡ ለመሆኑ፤ በዙሪያችን የከበበንን ግዘፋዊ ዓለም እና ግዘፋዊው ዓለም የሚነግረን ነገር እሙናዊ ነውን? እንዲህ ያለ ጥያቄ ለአንድ ገጣሚ ብናነሳለት፤ ‹‹አይ እነዚህ ነገሮች ከመንፈሳዊ ራዕይ የበለጠ ዕሙናዊ አይደሉም፡፡ የክሎዛፕ እይታዎች ናቸው እንጂ›› ሊል ይችላል፡፡
ገጣሚው ምን ማለቱ ነው? የምንዳስሰው እና በዙሪያችን ያለ ነገር በመንፈሳዊ ዕይታ (mystical vision) ከምንመለከተው ነገር በበለጠ ጎልቶ የሚሰማ ነው፡፡ ግን ያ ተጨባጭ ነገር ትርጉሙን ለመረዳት ያስቸግራል። በመንፈሳዊ ዕይታ ስናየው ግን የተሟላ እና ትርጉሙ ግልፅ ይሆንልናል፡፡ ከተሳግንበት የጊዜ እና የቦታ ቅርቃር ወጥተን፤ በሦስት የጊዜ አውታር ተቦጫጭቆ የነበረው ህልውና ከመቅጽበት አንድ ወጥ ሆኖ፤ ግዘፉ ዓለም ባዕድ እና ግራ አጋቢ መሆኑ ቀርቶ፤ መነሻ እና መድረሻው በውል የሚታወቅ፤ አስፈሪነቱ እና ግራ አጋቢነቱ ተወግዶ፤ ፍርሀትና ስጋት ጠፍቶ፤ ሁሉም ነገር ምላት አግኝቶ፤ የመኖራችን ትርጉም ሲገለጥልን ራሳችንን እና ዓለምን ይበልጥ እናውቀዋለን፡፡ እናም ጥያቄው፤ ‹‹የትኛው ነው እሙናዊ?›› የሚለው ነው፡፡ ይህችን እይታ የቀመሰ ገጣሚ ወይም ፈላስፋ ወይም ጻዲቅ፤ ያቺን የቅጽበት እይታ መልሶ ለማግኘት ይማስናል፣ አብዝቶ ይደክማል፡፡
ለጠቀስነው የስዌደንቦርጅ መጽሀፍ መግቢያ የጻፉት ኮሊን ዊልሰን እንደሚሉት፤ የ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ምርጥ ምርጥ ገጣሚያን እና የኪነጥበብ ሰዎች ያቺን የቅፅበት ዕይታ መልሶ ለማየት ሲዳክሩ፤ በመንፈስ ጣመን የሞቱ ብዙዎች ናቸው፡፡  ስለ ስዌደንቦርጅን ሌላ ጊዜ አጫውታችኋለሁ፡፡

Published in ህብረተሰብ
Saturday, 13 June 2015 14:53

የመምረጥ ነፃነት!

         ወደ እሳት ወይስ ወደ ውሃ?

       ህሊና ገዢ የሚሆንበትን ዓለም እንደ ኤግስቴንሺያሊዝም /ህልውናነት/ የፍልስፍና ዘወግ አራማጆች አብዝቶ የተመኘ የለም፡፡ ኤግስቲንሺያሊስት ከሓሳባዊያን እና ከቁስአካላዊያን ፍልስፍና አቀንቃኞች ለመለየታቸው የሚያስቀምጡት ድንበር ይኸው የፈረደበትን ህሊናን ነው፡፡ የሰው ልጅ በግዴታ ሕግ የማይገዛ ብቸኛ ፍጡር እንደሆነ እና ምርጫ እንጂ አድርግ አታድርግ ቀኖና ከላዩ ላይ እንዳአልተከመረበት በአምክንዮ የተደገፈ ትንታኔያቸውን ያቀርባሉ፡፡ ወደ ‘እሳት’ ወይም ወደ ‘ውኃ’ የሚለው ምርጫ ህሊና የሚመዘንበት ወይም የሚፈተንበት የኑባሬው ዓለም እውነታ ነው ይሉናል፡፡ ይህም አቋማቸው ከኃይማኖታዊ አስተምህሮት ጋር ኩታገጠም ቢያስመስላቸውም በውስጣቸው ግን የኢአማናዊነት (Atheism//ዝናባሌ ያላቸው በርካታ ፈላስፎችን እናገኛለን፡፡ የማርክሲዝም ሌኒኒዝም መዝገበ ቃላት በገጽ 11 ላይ የኤግስቴንሺያሊስቶችን አቋም በእዚህ መልኩ ያብራራል:-
“ህልውናነት /ኤግስቴንሺያሊዝም/ ሁለት አመለካከቶችን አጣምሮ የያዘ ነው፤ እነሱም ሃይማኖታዊ ህልውናነትና ኢእምነታዊ ህልውናነት ናቸው፡፡ የመጀመሪያው እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ሙሉ ነፃነት ሰጥቶታል የሚል ሲሆን ሁለተኛው እግዚአብሔር ባለመኖሩ ሰው ለሚሠራው ሁሉ ብቸኛ ተጠያቂ ነው ይላል፡፡”
በሁለቱም ጎራ የተሰለፉት የህልውናነት ፍልስፍና አራማጆች የመምረጥ ነፃነትን ለድርድር አያቀርቡም፡፡ ሰውን ሰው ያደረገው የመምረጥ ነፃነቱ ነው ይላሉ፡፡
በአብዛኛው ኃይማኖታዊ አስተምርሆት ዘንድ ህሊና በሥጋ ገዳም ውስጥ እንደመነኮሰ ጻዲቅ ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ ወደ እሳት አልያም ወደ ውኃ ሁለት አቻ እና ተቃርኖ ምርጫዎች (dialectical chioces) ከውልደት እስከ ሞት አብረው የሚዘልቁ ተገዳዳሪ ፈተናዎች ናቸው፡፡ የመንፈስ ነዲያንነትን ወይም ድህነትን ለመቀበል በምርጫው ላይ መጠበብ ግድ ይላል፡፡
እንግዲህ የሰው ልጅ ፈተና የሚጀምረው እዚህ ጋ ነው፣ ከሁለቱ ጫፎች ለአንዱ ልቡን መፍቀድ ይኖርበታል፡፡ አማካኝ የሚባል ነገር የለም፡፡
ይህ ዓይነት የምርጫ አጣብቂኝ በሌሎች ፍጡሮች ላይ አይስተዋልም፡፡ ደስታ እና ሐዘን፤ ለቅሶ እና ፈንጠዝያ፤ አዎንታዊ እና አሉታዊ ተብለው በተፈረጁ ተቃራኒ ጫፎች አበሳውን የሚያይ ፍጡር ከሰው ልጅ በስተቀር የለም፡፡ የሰማይ አእዋፋት አይዘሩም አያጭዱም፡፡ በልካቸው በተሰፋ ወጥ ሰብእና እየከነፉ፣ እየቦረቁ፣ ዘር እየተኩ ያከትማሉ፡፡
ኃይማኖት በሌላቸው ማኅበረሰብ ውስጥ ክፍፍሉን የሚፈጥረው ባህል ይሆናል፡፡ ነፍሰ ገዳይን ለሹመት በሚቀባ እና ሠላምን በሚሰብክ ባህል ውስጥ ሊኖር የሚችለው የእሳት እና ውሃ ፍረጃ ለየቅል ነው፡፡ ባህሉ የሚኮንነው በእሳትነት ሲፈረጅ፣ ባህሉ የሚያወድሰው ደግሞ በውሃ ይመሰላል፡፡ እዚህ ጋ ነው መደበላለቁ የሚመጣው፡፡
በእርግጥ ህሊና ከባህል እና ከኃይማኖት ክበብ ባሻገር ሚዛን የሚሰፍርበት መለኪያ ይኖረው ይሆን?
የምርጫ ነፃነትን፣ ቁስአካላዊው ፈላስፋ ቶማስ ሆብስ እንደ በረከት አይቆጥረውም፡፡ በሰው ልጅ የመምረጥ ነፃነት ላይ ገደብ እስካልተበጀ ድረስ ምድር የሰላም አየር ልትተነፍስ አትችልም ይላል፡፡ የምርጫ ነፃነት አጥፊነቱ እንዳይበዛ የግድ አንድ ሸባቢ ወይም ለጓሚ ኃይል /leviathan/ ከማኅበረሰቡ በላይ መሾም ይኖርበታል፡፡ ይህንን ሸባቢ ኃይል መንግሥት እያልን እንጠራዋለን፡፡ መንግሥት የሚባለው የፖለቲካ ኃይል እስካልተፈጠረ ድረስ የምርጫ ነፃነቱ ዋስትና ሊያገኝ አይችልም፡፡ ጉልበተኞች የራሳቸውን ፍላጎት በደካሞች ላይ ለመጫን በሚያደርጉት ሩጫ የእርስ በእርስ ፍልሚያ “all war against all” ውስጥ ይገባሉ፡፡
የመምረጥ ነፃነት እና ክልከላ
ክልከላ በሰው ልጅ የመምረጥ ነፃነት ግዛት ላይ የተተከለ ግንብ ነው፡፡ በእዚህም ምክንያት ከክልክላው፣ ከግንቡ ባሻገር ካለ ዓለም ጋር ለመወዳጀት በሚደረግ ግብግብ የተነሳ ትግሉ ይጦፋል፡፡ የተተከለው ግንብ በሚፈጥርብን ረሃብ መነሻ፣ ከጋሬጣው ወዲያ ያለውን ምስጢር ለመበርበር ልባችን ክፉኛ ይነሳሳል፡፡ ይኸም የመምረጥ ነፃነትን ኢ-ተፈጥሯዊ በሆነ ስልት በትንቅንቅ መተግበር እንችላለን ወደሚል አጥፊ አቋም እንድንሳብ ያስገድደናል፡፡ ትግል ደግሞ ማሳረጊያው መልካም አይደለም፡፡ በመናኛ ነገሮች ተሰነካክሎ መቅረትን፣ እንክትክት ብሎ ከእነአካቴው መሰባበርን ያስከትላል፡፡
ኮዬ የተባለ የስነ-ልቦና ባለሙያ “law of reverse effect” በሚለው ጽንሰ ሐሳብ ይህንን እውነታ ግልጽ አድርጎ አስቀምጦታል፡፡ ለምሳሌ ሳይክል መንዳት ገና የሚለማመድ ሰው፣ በሰፊ የአስፓልት ጎዳና ላይ እየተወዛወዘ እየነዳ ሳለ በአጋጣሚ አንዲት ጠጠር ከጎዳና ላይ ይመለከታል፡፡ ይህ ሰው ከመንዳቱ ሒደት ጋር አይደለም ቀልቡ፡፡ መላ ትኩረቱን ይህቺ ሚጢጢዬ ጠጠር ትወስደዋለች፡፡ ከጠጠሯ ጋር እጋጫለሁ አልጋጭም በሚል ሙግት ውስጥ ይገባል፡፡ በሰፊው ጎዳና ምትክ ይቺ ሚጢጢዬ ጠጠር ከአእምሮው ወለል ላይ ትነጠፋለች፡፡ በአአምሮ ዓለም ጠጠሯ የቋጥኝ ግርማ ሞገስን ተላብሳለች፡፡ በመጨረሻ ሄዶ ሄዶ ከእዚች ጠጠር ጋር መላተሙ አይቀሬ ይሆናል፡፡ ሚጢጢዬዋ ጠጠር በዳዊት ተመስላ እንደ ጎሊያድ ለዓይን የሚከብደውን ሳይክል ጋላቢ ከተቆናጠጠበት መቀመጫ  ላይ በአናቱ ትገለብጠዋለች፡፡
ልክ እንደ ምሳሌው በሕይወት ውስጥ የምንታገላቸው እዚህ ግቡ የማይባሉ ደቃቅ እውነታዎች እየጠለፉን ይጥሉናል፡፡ ነፃነት ሲያሸልብ ትግል ይነቃቃል፡፡ በሰውነት የተለገሰንን ምሉዕ ነፃነት የሚቀናቀን ሁነኛ እክል ሲገጥመን ያለን አማራጭ የተነፈግነውን፣ የተወሰደብንን መብት ለማስከበር ባገኘነው ቀዳዳ መውተርተር ይሆናል፡፡ ከዓይናችን የሚገቡ ሰላላ ቁምነገሮች በሙሉ የተከለከልነው ነፃነት ትሩፋቶች እየመሰሉን አቅላችንን እስክንጥል ድረስ ልንወዳጃቸው ክፉኛ እንጣደፋለን፡፡
በቤተሰብ ቅጣ ያጣ ቁጥጥር አበሳዋን ስትቆጥር የነበረች ኮረዳ ውጤት ቀንቷት ከትውልድ ቀዬዋ ራቅ ወዳለ አንዱ ዩኒቨርሲቲ ትገባለች። አሁን የመምረጥ ነጻነቷ በዋንኛነት የሚዘወረው በእርሷ ብቻ ይሆናል። እዚህ እግረ ሙቁ እንክትክት ብሎ ተሰባብሯል። ነፃ ግዛት ነጻ ድንበር። እንዳሻት ለመቦረቅ ልጓሟ ተፈቷል። ፈረሱም ሜዳውም ከፊቷ ቀርቧል፡፡
ኮረዳዋ ለመምረጥ ነፃነት ገና ወገቡ ያልጠና የሚደህ ጨቅላ ነች። ከመምረጥ ነፃነቷ ጋር በዓይነ ሥጋ ለመተያየት በስሜት መንጎድ ይሆናል የዘወትር ምሷ። የታመቀ የወሲብ ፍላጎቷን ለማፈንዳት ባገኘችው ሰፊ ግዛት ላይ እንዳሻት ትቦርቃለች። ይሄንንም ያንን ትጨብጣለች። ደስታው ዘላቂ ይመስላታል። ትንሽ እንደቆየች ግን ‘የእንቁራሪቷን’ ታሪካዊ ስህተት ትደግማለች።
እንቁራሪቷ በሚፈላ ውኃ ውስጥ እስከ 99 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በሙቀቱ ሀሴት እያደረገች ነው የምትዘልቀው። ከአንድ እስከ 99 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ውስጥ ያለው ዓለም ልዩ ነው። ውስጧ እየፋፋ፣ ፊቷ እየፈካ 99ኛው ዲግሪ ሴንቲግሬድ ላይ ትደርሳለች። ችግር የሚመጣው ከእዚህ በኋላ ባለው ዲግሪ ሴንቲግሬድ ላይ ነው። ልክ 100ኛው ዲግሪ ሴንቲግሬድ ላይ ሁሉ ነገር ይለወጣል፡፡ ከሕይወት ወደ ሞት ትሸጋገራለች። በደስታ ወጀብ ውስጥ ከግራ ቀኝ ስትፈስ በእያንዳንዷ ዲግሪ ሴንትግሬድ ወደ ሞት አፋፍ እየቀረበች እንደነበር ማን ይንገራት። ከእያንዳንዷ ዲግሪ ሴንቲግሬድ ደስታ በስተጀርባ የሞት ዘር እየፋፋ እንደሚሄድ ለመረዳት እንስሳዊ ተፈጥሮዋ ሊፈቅድላት አልቻለም፡፡
ኮረዳዋን ዝሙት፣ አሺሽ እና መጠጥ ያልጠበቀችው የደስታ ሕይወት ውስጥ ከትቷታል። ይሄንን ለማጣጣም ለዓመታት ጠብቃለች። በቤተሰብ ጥብቅ ቁጥጥር ቀልቧ ያዘዛትን ማድረግ ተስኗት ነበር። የነፃነት ሕይወትን በጽኑ ተርባ ስትጠባበቅ ኖረች። በመጨረሻም ከቤተሰብ የቁጥጥር ሕይወት ነፃ ሆነች። የመምረጥ ነፃነቷን ግን አንሻፋ ነው የተረዳችው፡፡ ድህረ ነጻነቷ በሚፈጥርላት ደስታ እየተመራች፣ ወደ መቶ ድግሪ ሴንቲግሬድ የሚያንደረድረውን ሀዲድ ትይዛለች፡፡ በማሳረጊያው ነፃነቷ እሳት ሆኖ ይበላታል፡፡
በእርግጥ የሰው ልጅ ህሊናው እየዳኘው ብቻ መኖር የሚችል ፍጡር ነው?
የመምረጥ ነፃነት በተከበረበት ማህበረሰብ ውስጥ የምናስተውላቸው የሰብዕና ዝቅጠቶች /Mental decadence/ ስንታዘብ፣ በሰው ልጅ ምሉዕነታችን ላይ ጥርጣሬ ይገባናል፡፡ ዓለም በህሊና ፍርጃ ብቻ መዳን አልቻለም፡፡ መረን የለቀቀ ወሲባዊ ግንኙነቶች /Homosexuality/፣ለመስማት ለማየት የሚቀፍ የለየለት ጭካኔ /Barbarian act/፣ ከቁስ ሰቀቀን ያልተላቀቁ አልጠግብ ባይ ገዢዎች የሚያደርሱት በደል በሙሉ የሰው ልጅ በህሊናው ብቻ እየተዳኘ መኖር የማይችል አቅመ ቢስ ፍጡር እንደሆነ ዋቢ ምስክሮች ናቸው፡፡
ይህንን ነጥብ በሌላ ጽንፍ ስንመለከተው ግን መደምደሚያችን በእጅጉ የተቃረነ ይሆናል። ለህሊና ዳኝነት ተገዢ ለመሆን የሕይወት መስዋዕትነትን እስከ መክፈል የደረሱ ሕያዊያንን ዓለማችን በየዘመኑ ስትታዘብ ኖራለች፡፡ ሶቅራጠስ መርዝ ከመጋቱ በፊት ከእስር ማምለጥ የሚችልበት ዕድል ተመቻችቶለት ነበር፡፡ ይህ ድብብቆሽ ግን እንደሶቅራጠስ ላለ ልዕለ ስብዕና ለተላበሰ ፍጡር የሚመጥን አልነበረም፡፡ የእርሱ ውጥን የጭቦውን ዓለም የሚገስጥበትን ህሊናውን ነፃ ማድረግ ነበር። “እኔ በሕይወት ኖሬ እውነት ከምታሸልብ፣ እኔ አሸልቤ እውነት ብትለመልም ይመረጣል” ብሎ ዕድሉን ያመቻቹለትን ባልንጀሮቹን ፊት ነሳቸው፡፡ በሞቱ ሕይወትን፣ በውሃው እሳቱን ድል ነሳው፡፡
የህሊና ልዕልና እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ድረስ የሚያስከፍል መራራ እውነትን መጋትን የሚጠይቅ ብርቱ ፈተናን ይጋብዛል፡፡ ወደ ‘እሳት’ ወይም ወደ ‘ውሃ’ የሰው ልጅ እድሜ ዘመኑን በሙሉ የሚፈተንበት እንቆቅልሽ ነው፡፡

Published in ህብረተሰብ
Saturday, 13 June 2015 14:51

የፀሐፍት ጥግ

የመፃፍ  ጥበብ የምታምንበትን የማግኘት ጥበብ ነው፡፡
ጉስታቬ ግሎበርት
ለእኔ የመፃፍ ታላቁ እርካታ የሚፃፈው ጉዳይ አይደለም፤ ቃላቱ የሚፈጥሩት ውስጣዊ ሙዚቃ ነው፡፡
ትሩማን ካፖቴ
ሃያሲ መገምገም የሚችለው ፀሐፊ የፃፈውን ሳይሆን እሱ ያነበበውን መፅሃፍ ብቻ ነው፡፡
ሚኞን ማክላውግህሊን
መፃፍ ከዝምታ ጋር የሚደረግ ትግል ነው፡፡
ካርሎስ ፉንቴስ
ፅሁፍ የዝምታና የብቸኝነት ውጤት ነው፡፡
ዋርዊክ ዩኒቨርሲቲ (1997)
ራሱን የማይመግብ አዕምሮ ራሱን ይበላል፡፡
ጎሬ ቪዳል
ማንም ቢሆን በፅሑፉ የቃለ አጋኖ ምልክት መጠቀም የለበትም፡፡ ያንን ማድረግ በራስህ ቀልድ እንደ መሳቅ ነው፡፡
ማርክ ትዌይን
ከሌላ ፀሃፊ ላይ ባለ ሁለት ቃላት ሃረግ ሰርቄ ከምያዝ ባንክ ስዘርፍ ብያዝ እመርጣለሁ፡፡
ጃክ ስሚዝ
እያንዳንዱ ቃላት ከውስጣዊ ፍላጎት ነው የሚወለደው፡፡ ፅሑፍ ፈፅሞ ከዚህ ውጭ መሆን የለበትም፡፡
ኢቲ ሂሌሱም
በፅሁፍ ሃብታም መሆን ከፈለግህ፣ ለራሳቸው ሲያነቡ ከንፈራቸውን ለሚያንቀሳቅሱ ሰዎች የሚሆን ነገር ፃፍ፡፡
ዶን ማርኪውስ
የመጀመሪያ ረቂቅህን በልብህ ፃፈው፡፡ ከዚያም በእጅህ ደግመህ ፃፈው፡፡
“Finding Forrester”
ከተሰኘው ፊልም
በልብ ወለድና በእውነታ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? ልብ ወለድ ስሜት መስጠት አለበት፡፡
ቶም ክላንሲ
ሰውም ሆነ እግዚአብሔር ምን መፃፍ እንዳለብኝ አይነግሩኝም፡፡
ጄምስ ቲ.
ከፅሁፍ ገንዘብ ማግኘት የሚቻለው በአንድ መንገድ ብቻ ነው፤ ይኸውም የአሳታሚ ሴት ልጅ በማግባት፡፡   
ጆርጅ ኦርዌል

Published in የግጥም ጥግ
Saturday, 13 June 2015 14:50

አሰቃቂው የእገታ ድራማ!

    በዓለም የእገታ ታሪክ አጋቾቹን ጨምሮ በርካታ ንፁሐን ታጋቾች ያለቁበት፤ መንግሥት እውነታውን ያፈነበትና መጨረሻው የዓለም ህዝብን በእንባ ያራጨ፣ አሰቃቂ እገታ የተፈፀመው እ.ኤ.አ በ2004 ዓ.ም በሩሲያ፣ ቤስላን ት/ቤት ውስጥ ነበር፡፡
የቤስላን ት/ቤት እገታ በጣም አሳዛኝ፣ አስደንጋጭና ቅስም-ሰባሪ በመሆን እስካሁን የሚወዳደረው የለም፡፡ ይህን የሶስት ቀን “ሲኦል” አለምን ባስደነገጠ ሁኔታ የተረኩት ከእገታው የተረፉ ሌሎች የአይን እማኞች ናቸው፡፡ ነገር ግን የሩሲያ መንግሥት በወቅቱ የሰጠው መግለጫ ከእማኞቹ ጋር ፈፅሞ የማይገናኝና የተጣረሰ ነበር። እገታውን ያደረጉት አረቦች ወይም “አለም አቀፍ አሸባሪዎች” ናቸው የሚለው የክሬምሊን መግለጫ ሃሰት እንደነበር የታወቀው ኋላ ላይ ነው። አጋቾቹ ሩሲያ በቺቺኒያ ውስጥ ያሰፈረችውን ጦር እንድታስወጣ ግፊት ሲያደርጉ የነበሩ የቺቺኒያ አማፅያኖች እንደሆኑ ታውቋል፡፡
የቺቺኒያ አማፅያኖች ናቸው የሚለውን የሩሲያ መንግስት ቢያስተባብልም ከእገታው በህይወት የተረፉ እማኞች ግን አጋቾቹ ሲያወሩ የነበረው በራሺያ ቋንቋ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ከቤስላን ብዙም ከማትርቀው የኢንጉሽ ብሔር የመጡ ናቸው ብለዋል፡፡ ሌሎች እማኞች ደግሞ የስላቪክ ሚሲዮናዊያን እንደሆኑ ገልፀው ነበር፡፡
የቤስላን ት/ቤት እገታን የበለጠ አደናጋሪ ያደረገው ግን በእገታው ድራማ በአጠቃላይ የሞቱት ሰዎች ቁጥር መዋዠቅ ነው፡፡ በመንግሥት በኩል 360 ታጋቾችና 30 አጋቾች እንደሞቱ ተነግሮ ነበር፡፡ ነገር ግን በሁከቱ ወቅት በአካባቢው የነበሩ ጋዜጠኞች ከ400 በላይ አስክሬኖችን አይተናል ሲሉ ዘግበዋል፡፡ 200 የሚሆኑ ቤተዘመዶች መርዶ እንዳልደረሳቸው የሀገሬው ቀይ-መስቀል አሳውቆ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ 90 አስከሬኖች ገና በምርመራ ላይ እንዳሉ የመንግሥት ባለስልጣናት ተናግረው ነበር፡፡ የሟቾቹ ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን የምንገነዘበው ግን 38 የተበጣጠሱ አስከሬኖች መለቀማቸውን ስንረዳ ነው፡፡
ስለ እገታው ከተነገሩት ውስጥ ትልቁን ቦታ የሚይዘው፣ እገታው በአሳዛኝ መልኩ እንዲጠናቀቅ ያደረጉት ራሳቸው የመንግስት ባለስልጣናት ናቸው የሚለው ነው፡፡ በህይወት የተረፉ እማኞች፤ አጋቾቹ ከባለስልጣናቱ ጋር የመደራደር እድል እንዳላገኙ እንባ በተቀላቀለበት ምሬት ተናግረዋል፡፡ ፖሊሶች በማንኛውም ደቂቃ የት/ቤቱን ህንፃ ሰብረው ይገባሉ በሚል ስጋት አጋቾቹ ዘወትር ይነጫነጩ እንደነበር እማኞቹ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
እገታው ምንአልባት በአሳዛኝ መልኩ ከተጠናቀቀ በሚል ፍራቻ የሩሲያ መንግስት የታጋቾቹን ቁጥር ወደ 354 አውርዶትም ነበር፡፡ የታጋቾቹ ትክክለኛ ቁጥር ግን 1200 እንደነበር በኋላ ላይ ተጋልጧል፡፡ (በመለቀቂያ ሰዓት ተማሪ ልጆቻቸውን ለመውሰድ ግቢው ውስጥ የገቡ ብዙ ወላጆችም አብረው ታግተዋል) በእገታው ወቅት ከሶስት ተማሪዎች ጋር በት/ቤቱ ጂምናዚየም ውስጥ ተደብቃ የነበረችው መምህር ማርጋሬት ኮምየቫ ስለሁኔታው ስትገልፅ፤ “አጋቾቹ በባለስልጣናት የተነገረውን የታጋቾች ቁጥር ሲሰሙ በጣም ተበሳጭተው ነበር፤ እንዲህ ያሉት ወደኛ ሰብረው ለመግባት ስለሆነ ለሞት ተዘጋጁ! ብለውን ነበር” ብላለች፡፡
አርብ ጧት ፀሐይ ከመውጣቷ በፊት የእገታው ውጥረት ተባብሶ ጫፍ ላይ ደረሰ፡፡ ከአንድ ቀን በፊት ታጣቂዎቹ (አጋቾቹ) ከኢንጉሺቲያ ፕሬዚዳንት ረስላን አውሼቭ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ የተወሰኑ ህፃናትን ከእናታቸው ጋር አብረው ለቀው ነበር፡፡ ከጧቱ አንድ ሰዓት ላይ ግን ሁሉም ነገር ውጥንቅጡ ወጣ፡፡ አጋቾቹ ት/ቤቱን ከበው በቆሙት ፖሊሶች ላይ የእጅ ቦንቦችን በመስኮት በመወርወር በአንድ አዛዥ ላይ ከባድ ጉዳት አደረሱ፡፡
ከሰዓት በኋላ ደግሞ መስኮት ላይ አስቀምጠዋቸው የነበሩትን ሌሎች ቦንቦች በማሰናዳት ተጨማሪ ጥቃት ለመሰንዘር ራሳቸውን አዘጋጁ፡፡ ይህን የተመለከቱት ታጋቾች ከፍተኛ ፍርሐት ስለዋጣቸው ሳያስቡት ትርምስና ሁከት ፈጠሩ፡፡ ነገር ግን ከታጣቂዎቹ ቁጥጥር ውጭ ባለመሆናቸው መልሰው አደብ ገዙ፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር ታጣቂዎቹ ትንንሽ ልጆችን መርጠው መስኮት ላይ በማቆም የሰው ጋሻ ያደረጓቸው፡፡ ማንም ህፃን ከቆመበት ውልፊት ቢል እጣ-ፈንታው ሞት እንደሚሆንም በአስፈሪ ድምፅ ተነገራቸው፡፡
ህፃናቶቹ ከአንድ ቀን ቀደም ብሎ የውሃ ጥማቸውን በለቅሶ ገልፀው ነበር፡፡ አሁን ግን በታጣቂዎቹ ጭካኔ በመደናገጣቸው ተጨማሪ ጥማቸውን በዝምታ ለማጣጣም ተገደዱ፡፡ በዚህ ቅፅበት ነበር ጥቂት ታጋቾች ቀጥሎ የሚከሰተው አደጋ ስለገባቸው፣ ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ለማትረፍ ሲሉ ወደ መውጫው በር የተንፏቀቁት። ከእገታው በህይወት የተረፉትም ይህን እርምጃ የወሰዱት ነበሩ፡፡
የታጣቂዎቹ ዋና መሪ በተከታዮቹ ዘንድ “ኮሎኔል” በሚል ማዕረግ ነበር የሚጠራው። “ኮሎኔል ከህንፃው ውጭ ካለ አንድ ሰው ጋር በሞባይል ሲያወራ በራሺያ ቋንቋ ነበር” ያሉት የ65 ዓመት ታጋች አያት የነበሩት ዛራ ሜድዜቭ ናቸው። “ኮሎኔል ሲያወራ የነበረው ከመንግሥት ተደራዳሪ ባለስልጣን ጋር ነበር፡፡
“የጠየቃችሁንን በሙሉ ፈፅመናል፣ ከዚህ በላይ ምን ፍጠሩ ነው የምትሉን?” በማለት በንዴት ጦፈ። በስልክ የተሰጠው ምላሽ እንዳላረካው ያስታውቅ ነበር፡፡ ሲነጋገርበት የነበረውን ሞባይል መሬት ላይ በብሽቀት ጥሎ፤ “ከዚህ በላይ ምን እንድንጠብቅ ይፈልጋሉ?” በማለት ተወራጨ፡፡
ከምሽቱ አንድ ሰዓት ላይ ግን እገታውን አስቀያሚ ያደረገና ወለሉን በደም ያጨቀየ ክፉ ክስተት ተፈጠረ፡፡ ከጂምናዚየሙ ምዕራብ  በኩል አንድ ከባድ ፍንዳታ ተሰማ፡፡ ይህን ፍንዳታ ተከትሎ የተበጣጠሱ የሰው አካሎች አየር ላይ እየተንሳፈፉ ከወለሉ ላይ ተበታትነው ተዘረገፉ፡፡
የሰው ጋሻ ተደርገው መስኮት ላይ ከቆሙት ህጻናቶች መካከል የ12 ዓመቱ ሶስላን ቤቴየቭ ይገኝበታል፡፡ ሶስላን ስለ ከባድ ፍንዳታው ሲናገር፤ “ከቆምኩበት መስኮት ላይ ልወርድ ስል አንድ አስደንጋጭ ፍንዳታ ተከሰተ፡፡ በፍንዳታው ሞገድ ተገፍትሬ ህፃናቶቹ ላይ ወደኩባቸው፡፡ ለመነሳት እየታገልኩ ሳለ ሌላ አስደንጋጭ ፍንዳታ ተከተለ። ሁሉም ሰው ነፍሱን ለማዳን በየአቅጣጫው በመራወጡ ቤቱ በሽብር ተሞላ” ብሏል፡፡ ሶስላን ይህን ሲናገር፣ ሐሳቡን መረዳት እስኪያዳግት ድረስ ይርበተበትና ይጣደፍ ነበር፡፡ በአእምሮው ውስጥ ያሉትን ሚሊዮን ቃላቶች ለማውጣት ከመጣደፉ የተነሳ ንግግሮቹን እርስ በርስ ያጠላልፋቸው ነበር፡፡
ሶስላን ከወደቀበት እንደምንም ተነስቶ በመስኮቱ ተንጠላጥሎ፣ በት/ቤቱ ጓሮ በኩል ወደ ታች ወረደ። እንደሱ በመስኮቱ ተንጠልጥለው ከወጡ ሁለት ሴት ተማሪዎች ጋር በመሆን ሮጠ፡፡ “ከጀርባችን በኩል ብዙ ጥይቶች ተተኮሱብን” ብሏል፤ ሶስላን ክንዱና ጀርባው ላይ ያሉትን ሁለት ቁስሎች እያሳየ። “አሁን ድረስ ቁስሉ እያሰቃየኝ ነው” አለ ህፃኑ ሲቃ እየተናነቀው፡፡ ነገር ግን ከሁለቱ አካላዊ ቁስሎች በላይ ሶስላንን ያሰቃየው በህፃን አእምሮው ላይ የደረሰው ውድመት ነበር፡፡
ከጂምናዚየሙ ውጭ ት/ቤቱን ከበው የቆሙት ፖሊሶችና ብዙ ሰዎች የመጀመሪያውን ፍንዳታ ተከትሎ ነበር የታጋቾቹን ትርምስና ጩኸት የሰሙት። ከዚህ በኋላ ፖሊሶች ህንፃውን ሰብረው እንደሚገቡ አጋቾቹ እርግጠኛ ነበሩ፡፡ ይህ መላምታቸውም ተስፋ እንዲቆርጡ አደረጋቸው። በመሆኑም በአደጋ ሰራተኞችና በታጋቾች ላይ ጥይት በማዝነብ የመጨረሻ እልኻቸውን ተወጡ። ይህን ተከትሎ ግን ህንፃውን ለመቆጣጠር ምንም አይነት እቅድ ያላወጡት የፀጥታ ኃይሎች፤ ድንገት ወደ ውስጥ ዘው ብለው ገቡ፡፡ ይህ የፀጥታ ኃይሎች አቦ-ሰጥ ተግባር፣ የበርካታ ንፁሐን ታጋቾች ህይወትን ነጠቀ፡፡ አጋችና ታጋች ሳይለዩ በህንፃው ውስጥ ያሉትን በርካታ ሰዎች ገደሉ፡፡ የቦንቦች ፍንዳታና የተፈጠረው እሳት ብዙ ነፍሶችን በላ። በስፍራው የነበረ አንድ የውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ኦፊሰር፤ “የፀጥታ ኃይሎች ሰዎችን ከማዳን ይልቅ የጅምላ ውድመት ነው ያደረሱት” በማለት አሳዛኙን ክስተት ገልፆታል፡፡
ሁለተኛው ፍንዳታ በተከሰተበት ወቅት ታጣቂዎቹ ከሞት የተረፉ ሰዎችን ከየስርቻው በማሰባሰብ የመጨረሻ እቅዳቸውን ለመፈፀም ተዘጋጅተው ነበር፡፡ ሚስተር ሳጎሎቭ በዚህ ወቅት ከመጋረጃው ጀርባ ራሱን ሸሽጎ ነበር፡፡ ነገር ግን በታጣቂዎቹ አደና ተይዞ ካፍቴሪያ ውስጥ ከተከማቹ ታጋቾች ጋር ተወረወረ፡፡
“ከዚህ ተነሱ …. ሁላችሁም ተንቀሳቀሱ! … አለበለዚያ እንገድላችኋለን!” በማለት አምባረቁብን ያለው እጁ ላይ የቆሰለው የ13 ዓመቱ ታዳጊ ተማሪ ማርጂቭ ነው፡፡ “እኛን ያስፈራን ወለሉ ላይ የተዘረሩ በድን የሰው አካላት እየረጋገጡ ማለፍ ነው፡፡ ነገር ግን በታጣቂዎቹ አስገዳጅነት ገና መንገድ እንደጀመርን ከውጭ በኩል የተተኮሰ መዓት ጥይቶች እላያችን ላይ ዘነቡ፡፡”
ማርጂቭ ከነዚህ ጥይቶች ሊተርፍ የቻለው ከምድጃው በስተጀርባ በኩል በመተኛቱ ነበር። ይህን ተከትሎም አጋቾቹ ጊዜ ሳያጠፉ ህፃናቶቹን መስኮት ላይ በማቆም ነጭ ልብስ እንዲያውለበልቡ አስገደዷቸው፡፡ ይህን የማያደርግ ህፃን እንደሚገደልም አምርረው ተናገሩ፡፡ አንዲት ታዳጊ ተማሪ የታጣቂዎቹን ትእዛዝ ለመፈፀም ገና በጉልበቷ እንደቆመች፣ ከውጭ በኩል በተተኮሱ ሁለት ጥይቶች ደረቷ ላይ ተመታ ወደቀች፡፡ ማርጂቭ የሚያውቃት ዛውር ቢትሲቭ የተባለች ሌላ የ8 ዓመት ተማሪ፣ ከካፍቴሪያው ውስጥ በተተኮሰ ጥይት ጀርባዋ ላይ ተመትታ ህይወቷ አልፏል፡፡ ከታጣቂዎቹና ከፀጥታ ኃይሎቹ በኩል የሚተኮሱ የተዘበራረቁ ጥይቶች ህፃናቱን እንደ ጉድ አረገፏቸው፡፡
የሩሲያ ልዩ ኃይል ኦፊሰር፣ ቫስኖክ በመስኮት አንገቱን አዝልቆ፣ ማርጂቭ ሮጦ እንዲያመልጥ በተናገረበት ቅፅበት፣ ማዕድ ቤት ውስጥ በተደበቀ የቺቺን ታጣቂ ተገደለ። ቫስኖክ በጥይት እንደተመታ ሰውነቱ ያረፈው ከማርጂቭ የህፃን አካል ላይ ነበር፡፡ ማርጂቭ እንደተናገረው ከሆነ ተከታትለው የተተኮሱትን ጥይቶች ያበረደለት የኦፊሰሩ በድን ሰውነት ነው፡፡ የኦፊሰሩ አስከሬን የጥይት መከላከያ በመሆን የማርጂቭ ህይወትን ታደገ፡፡
የሩሲያ የውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ቪታሊ፣ እገታው ከጀመረበት ቀን አንስቶ ጂምናዚየሙ አካባቢ ቆሞ ነበር፡፡
ቪታሊ ሲቃ እየተናነቀው ስለሁኔታው ሲናገር፤ “የወጣቶችና የህፃናት ሙት አካሎች በጂምናዚየሙ ውስጥ ተበታትነው ስመለከት ራሴን ጠላሁ፡፡ በአዳራሹ ውስጥ የተነሳው ቃጠሎ የታጋቾቹን ማንነት መለየት እስኪያቅተን ድረስ ከህንፃው ጋር አብሮ አክስሏቸዋል፡፡ የዚህ አይነቱ አሳዛኝ ነገር በህይወቴ ሲገጥመኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።” ብሏል፡፡
በዚህ የጅምላ እልቂት የሞት ሰለባ የሆኑት ታጋቾች ብቻ ሳይሆኑ ራሳቸው አጋቾቹ ጭምር ናቸው፡፡ አንዳንድ እድለኞች ከጥይት ዝናብ ቢተርፉም ከቃጠሎው ግን መትረፍ አልቻሉም፡፡
አጋቾቹ የቤስላን ት/ቤት ያገቱበት ዋና ምክንያት በሩሲያና በቺቺኒያ መካከል የተከፈተው ጦርነት እንዲያበቃ ለማስገደድ ነበር፡፡ ከዚያ በተጨማሪ ግን በሩሲያ መንግሥት የታሰሩ 24 አማፅያኖች እንዲለቀቁም ጠይቀዋል፡፡ ከአጋቾቹ መካከል 10 አረቦች አሉበት የሚለው የክሬምሊን መግለጫ በፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ቢስተጋባም ቅሉ አቃቤ - ህጉ ጄኔራል ቭላድሚር ኡስቲኖቭ፤ በአስከሬን ምርመራ ወቅት አንድም አረብ አላገኘንም ብሏል፡፡   

Published in ህብረተሰብ
Page 10 of 16