ሃሳባችንን በነፃነት በመግለፃችን ነው ከስራ የታገድነው፡፡ - ጋዜጠኞች  

ከአዲስ አበባና የዙሪያዋ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ የኦሮሚያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ባካሄደው ግምገማ 20 ጋዜጠኞችን “ጠባብ የፖለቲካ አመለካከት አላችሁ” በሚል ገምግሞ ከሥራ ማገዱን ምንጮች ገለፁ፡፡ በማስተር ፕላኑ ዙሪያ በሚያዚያ ወር ፖለቲከኞች፣ ባለስልጣናትና ጋዜጠኞች የተሳተፉበት ውይይት በአዳማ ናዝሬት ተካሂዶ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፤ በማስተር ፕላኑ ዙሪያ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲዎች እንዲሁም በርካታ ከተሞች ተቃውሞና ረብሻ ከተከሰተ በኋላም ስብሰባዎችና ግምገማዎች በብዛት ቀጥለዋል፡፡
በሚያዚያ ወር በተካሄደው የአዳማ ውይይት ላይ ማስተር ፕላኑን በተመለከተ በርካታ ጋዜጠኞች የተለያዩ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን እንደሰነዘሩ የጠቀሱት ምንጮች፤ በማስተር ፕላኑ፣ በወቅታዊ ጉዳዮችና በሚዲያ ነፃነት ዙሪያ ለሁለት ወር በዘለቀው የጋዜጠኞች ስልጠና ላይም ተመሳሳይ ሀሳብና ጥያቄዎች እንደተሰነዘሩ ገልፀዋል፡፡
ስልጠናው ከተጠናቀቀ በኋላ ባለፈው ረቡዕ ወደ ሥራ ሊገቡ ሲሉ ወደ ግቢው አትገቡም ተብለው መከልከላቸውን የጠቀሱት ጋዜጠኞቹ፤ በስልጠናው ላይ በተነሱ ወቅታዊና አገራዊ ጉዳዮች ላይ ሃሳባችንን በነፃነት በመግለፃችን ነው ከስራ የታገድነው ሲሉ ተቃውመዋል፡፡
ቀደም ሲል በማስተር ፕላኑ ላይ በተካሄደ ውይይት ጋዜጠኞቹ ጉዳዩን ወደ ህብረተሰቡ ለማስረጽ እንደሚቸገሩና ህዝቡም በጄ ብሎ እንደማይቀበላቸው በመግለፅ አወያዮቹን መገዳደራቸውን ተከትሎ “ጠባብ የፖለቲካ አመለካከት አላችሁ” የሚል ትችት እንደተሰነዘረባቸው ምንጮቹ ጠቁመዋል፡፡ ማስተር ፕላኑን በመቃወም የተነሳውን ረብሻ የፀጥታ ሃይሎች ጥይት በመተኮስ ሳይሆን አስለቃሽ ጭስ በመጠቀም መቆጣጠር ነበረባቸው በማለት ተናግረናል ብሏል ከታገዱት ጋዜጠኞች አንዱ፡፡ የኦሮሚያ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት ጋዜጠኞቹን ያገደበትን ምክንያት እንዲገልፅልን ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም፡፡ ከአዲስ አበባና ዙሪያዋ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ ባለፈው ሚያዚያ ወር የተጀመረው ውይይት አሁንም በተለያዩ አካባቢዎች መቀጠሉን ለማወቅ ተችሏል፡፡

Published in ዜና

ሰልፉ የተከለከለው ብዙ ህዝብ ይወጣል በሚል ስጋት ነው - ፓርቲው

ዓረና አንድነትና ለልዑላዊነት ፓርቲ፤ “ፍትህና ውሃ ያስፈልገናል” በሚል መሪ ቃል በዛሬው ዕለት በመቀሌ ከተማ ሊያካሂድ የነበረው ሰላማዊ ሠልፍ “የፖሊስ ሀይል የለንም” በሚል እንዲሰረዝ መደረጉን የፓርቲው አመራር አቶ አብርሃ ደስታ ለአዲስ አድማስ ገለፁ፡፡
ቀደም ብሎ ለሰላማዊ ሰልፉ የከተማው አስተዳደር ፈቃድ ሰጥቷቸው እንደነበር የጠቆሙት አቶ አብርሃ፤ የቅስቀሳ ስራዎችን ጨምሮ መጠነ ሰፊ ዝግጅት ካደረግን በኋላ በትናንትናው ዕለት ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ የክልከላ ደብዳቤ እንደደረሳቸው ገልፀዋል፡፡
በትግራይ ክልል በመቀሌ ከተማ የመጀመሪያውን ጠንካራ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ አቅደን ነበር ያሉት አቶ አብርሃ፤ በሰላማዊ ሰልፉ ላይ የውሃና የፍትህ እጦት ጥያቄዎች እንዲሁም “ፍትህ በጠየቅን አሸባሪዎች አይደለንም” በሚል መንግስት በሚከተለው የሽብር አቋም ላይ ተቃውሞ ለማሰማት ታስቦ ነበር ብለዋል፡፡
የከተማው አስተዳደር ለፓርቲው በደብዳቤ በሰጠው ምላሽ፤ ሰላማዊ ሰልፉ የተሰረዘው በመቀሌ ከተማ ከሰኞ ጀምሮ ከሚከበረው “የሲቪል ሰርቪስ ሳምንት ቀን” ጋር በተያያዘ በቂ የፖሊስና ልዩ ሃይል ስለሌለን ነው ብሏል፡፡ ዛሬ ሊካሄድ ታቅዶ በነበረው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ከ5ሺ ሰዎች በላይ እንደሚገኙ ይጠበቅ ነበር ያሉት አቶ አብርሃ፤ ሰልፉ የተከለከለውም ብዙ ህዝብ ይወጣል በሚል ስጋት እንደሆነ የመንግስት ምንጮቻችን ነግረውናል ብለዋል፡፡

Published in ዜና

ጠቋሚዎች ህይወታችን ለአደጋ ተጋልጧል አሉ

በመንግስት የልማት ድርጅትነት የተመዘገበው የእለት ደራሽ የእርዳታ ትራንስፖርት ድርጅት ለከፍተኛ ሙስና መጋለጡን የገለፁ ጠቋሚዎች፤ ጉዳዩን ለፀረ-ሙስና ኮሚሽን በተደጋጋሚ ቢያሳውቁም እስካሁን መፍትሄ አለማግኘታቸውን፤ ህጋዊ ከለላ እንዳልተሰጣቸውም ተናግረዋል፡፡
ግዢዎች ያለጨረታና ትክክለኛ ባልሆኑ የጨረታ ሂደቶች ከመፈፀማቸውም በተጨማሪ፣ ጭነት ከማስጫን ጋር በተገናኘ የሂሳብ ማወራረጂያ ደጋፊ ሰነዶች በተለያየ ጊዜ በማጥፋት ብቻ ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ተመዝብሯል የሚሉት ጠቋሚዎቹ፤ በህገ ወጥ መንገድ በድርጅቱ ውስጥ በተቀጠረ ግለሰብ አማካይነት ከመለዋወጫ እቃዎች ጋር በተያያዘ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ መመዝበሩንና በወቅቱ ለሚመለከተው አካል ቢያመለክቱም ጉዳዩ ተድበስብሶ መቅረቱን ይናገራሉ፡፡
የድርጅቱ በርካታ ተሽከርካሪዎችም የግለሰቦች የግል መጠቀሚያ ሆነዋል ይላሉ፤ ጠቋሚዎቹ፡፡ ህገወጥ ግዢዎች እንደሚከናወኑ በመግለጽም በርካታ ዝርፊያ ይፈፀማል ባይ ናቸው፡፡ ያለጨረታ በተከናወነ የኢንጀክሽን ፓምፕ ግዢ 107 ሺህ ብር እንዲሁም  ከችቡድ ግዢ ጋር በተያያዘ 119 ሺህ ብር ተመዝብሯል ያሉት ጠቋሚዎቹ፤ ይሄንንም በማስረጃ አስደግፈን ለፀረ - ሙስና ብናቀርብም እርምጃ አልተወሰደም ብለዋል፡፡
ተሽከርካሪዎች በተለያዩ ምክንያቶች ከአገልግሎት ውጪ ሲሆኑ በካኒቫላይዜሽን ስርአት አስፈላጊ የመለዋወጫ እቃዎችን በመፍታት ለሌሎች ተሽከርካሪዎች እንዲውል ይደረጋል የሚሉት ጠቋሚዎቹ፤ በድርጅቱ መመሪያ መሰረት ካኒቫላይዜሽን ለመፈፀም የቦርድ ውሳኔ የሚያስፈልግ ቢሆንም ከመመሪያ ውጪ እየተሰራ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ንብረት የት እንደገባ አይታወቅም፤ ለዚህም ማስረጃዎች አሉን ብለዋል፡፡
የጭነት ማዘዣ ሰነዶችን፣ የነዳጅ መጠየቂያ ፓዶች (ደረሰኞች) ሆን ብሎ በማጥፋትም በብዙ ሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ መመዝበሩን እናውቃለን ይላሉ፡፡ በእጃችን የገቡ የሙስና ተግባሮችን ማስረጃ በመያዝና ከኪሳችን ገንዘብ እያወጣን ፎቶ ኮፒ በማድረግ ለፀረሙስና ኮሚሽን ብናስገባም ጥቆማችን ዋጋ ሳያገኝ እኛንም ለጥቃት ዳርጐናል ሲሉ ምሬታቸውን ገልፀዋል - ጥቆማ አቅራቢዎቹ፡፡
በቅርቡ የድርጅቱ የፋይናንስ ሁኔታ በውጭ ኦዲተሮች ተመርምሮ ድርጅቱ የግዥ መመሪያ አፈፃፀም መመሪያን፣ የግዥ እቅድ በተሟላ መልኩ እንደሌለው፣ የጨረታ ውጤት በጨረታው ለተሳተፉ ተጫራቾች ሆን ተብሎ በጽሑፍ እንደማይገለጽ የሚሉትን ጨምሮ   25 ሚሊየን ብር የሚጠጋ የመንግስት ገንዘብ መጉደሉ ተረጋግጦ ነበር የሚሉት ጠቋሚዎቹ፤  ሰሞኑን ደግሞ የጎደለው ገንዘብ መሟላቱን የስራ ኃላፊዎቹ ለኦዲተሮቹ እየገለፁ ነው ብለዋል፡፡
እነዚህን የመሳሰሉ የሙስና ድርጊቶችን በየጊዜው ለማጋለጥ በመሞከሬ ሁለት ጊዜ በጥይት  የግድያ ሙከራ ተደርጐብኝ ተርፌአለሁ ያሉት የህግ ክፍል ኃላፊው አቶ ያለው አክሊሉ፤ “የላባችን ዋጋ የሆነውን የወር ደመወዝ በየጊዜው ከመቁረጥ ጀምሮ ወከባ፣ ዛቻ፣ መገለልና ለስነ ልቦና ቀውስ እንድንጋለጥ ብሎም ተማረን እንድንለቅ የተቀነባበረ ሴራ እየተፈፀመብን ነው” ብለዋል፡፡
ባለፈው ሰኔ 6 ቀን 2006 ዓ.ም ለመጨረሻ ጊዜ በሚል ለፀረ ሙስና ኮሚሽን ለዳይሬክተሩ ዳይሬክተር ጥቆማቸውን እንዳቀረቡ የጠቆሙት የድርጅቱ የህግ ክፍል ኃላፊ አቶ ያለው አክሊሉ፣ የድርጅቱ የሥነ ምግባር መኮንን አቶ ሰማኸኝ ተፈሪና የድርጅቱ መሰረታዊ ሰራተኛ ማህበር ም/ሊቀመንበር አቶ መንግስቱ ሞላ፤ ዳይሬክተሩም “እኛ እንዲህ አድርጉ፣ አታድርጉ እያልን ማባበልና መለመን ሰልችቶናል፤ ከአሁን በኋላ የመጨረሻ እርምጃ ለመውሰድ ተዘጋጅተናል” በማለት እንደሸኟቸው ይናገራሉ፡፡ ሆኖም እስካሁን ምንም እርምጃ እንዳልተወሰደና ህይወታቸው ይበልጥ ለአደጋ እየተጋለጠ እንደመጣ ገልፀዋል - ጠቋሚዎቹ፡፡  
የእለት ደራሽ እርዳታ ድርጅት ስራ አስኪያጅ አቶ ጀማል መሃመድን አግኝተን ለማነጋገር ጥረት ብናደርግም በፀሃፊያቸው በኩል ስብሰባ ላይ ናቸው የሚል ምላሽ የተሰጠን ሲሆን በሞባይል እጅ ስልካቸው ላይ በተደጋጋሚ ብንደውልም ስልካቸው ባለመነሳቱ ሊሳካልን አልቻለም፡፡
የፌደራል የስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን የስነ-ምግባር የትምህርት እና ስልጠና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ አሰፋን ስለጉዳዩ ጠይቀናቸው፤ ጥቆማዎቹን በተመለከተ ምንም መረጃ እንደሌላቸው ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡

Published in ዜና

መንግስት፣ በየጊዜው “የምስራች” እያለ የሚነግረንን ወሬ ማመን ቢቀርብን ይሻላል። ግን፣ መስማትና ማመን ለምዶብናል፡፡ መልካም ነገር ስለምንመኝ ይሆን፤ “ለማመን” የምንቸኩለው? መንግስት አዲስ ወሬ ሲያበስረን እንሰማዋለን፤ “የዛሬውስ እውነት ሊሆን ይችላል” ብለን እናምነዋለን፡፡ ሌላው ይቅርና፤ “ኢትዮጵያ በእህል ምርት ራሷን ችላለች” ሲለን እንኳ አምነነዋል። በየጎዳናው የምናየው ድህነትና በየጓዳው የሚያጋጥመን የኑሮ ችግር በጣም ከባድና አሳዛኝ እንደሆነ ብናውቅም፤ የምስራች ሲበሰር ቶሎ ለማመን ዝግጁ ነን።
ምን ዋጋ አለው? ዳቦ ቤቶች በስንዴ እጥረት እንደ ዘንድሮ ተቸግረው አያውቁም፡፡ ባለፈው ጥቅምት ወር ገደማ ነው ነገሩ የተጀመረው። “አዝመራው ጥሩ ምርት ይዟል” ተባለ በደፈናው፡፡ ግን በዚሁ ተደፋፍኖ አልቀረም፡፡ በእህል አይነት እየተዘረዘረ፤ ከነመጠኑ በኩንታል እየተጠቀሰ  “ከፍተኛ የእህል ምርት ይሰበሰባል” የሚል የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለስልጣን ሪፖርት ወጣ። ይህን ሪፖርት ተከትሎ፤ የእህል ንግድ ድርጅት መግለጫ ለመስጠት ቀናት አልፈጀበትም። ስንዴ ከውጭ ለመግዛት ነው ወራት የሚፈጅበት፡፡
የእህል ገበያ ድርጅት ሃላፊዎች፤ የእህል ምርት በብዛት እንደሚሰበሰብ በመጥቀስ ታህሳስ ወር ላይ በሰጡት መግለጫ፤ የእህል ዋጋ አሽቆልቁሎ ገበሬዎች ተጎጂ እንዳይሆኑ እንሰጋለን በማለት ጭንቀታቸውን አስረድተዋል።
እንዲያውም፣ የእህል ዋጋ ገና ካሁኑ የመቀነስ አዝማሚያ ጀማምሮታል በማለት የተናገሩት የድርጅቱ ሃላፊዎች፣ ለምሳሌ የጤፍ ዋጋ በኩንታል 20 ብር ቀንሷል በማለት ማስረጃ አቅርበዋል፡፡ የአንድ ኪሎ የጤፍ ዋጋ ላይ የሃያ ሳንቲም ቅናሽ መታየቱ እንደ ትልቅ ነገር መወራቱ አያስገርምም? ይሄም ብቻ አይደለም፡፡ በየአመቱ ከታህሳስና ከጥር ወር በኋላ የእህል ዋጋ እንደሚጨምር እንዴት ይዘነጉታል? ለዚያውም “የእህል ንግድ” ላይ የተሰማሩ ሃላፊዎች ናቸው!
ለማንኛውም የእነሱ ጭንቀት፣ የእህል ምርት “ተትረፍርፎ” ገበያ ላይ ዋጋው እንዳይወድቅ ነው። ደግነቱ፤ ችግር የለም፡፡ ችግር አይፈጠርም። የእህል ንግድ ድርጅት አለልን፡፡  ሃላፊዎቹ፤ እህል በመግዛትና በመሰብሰብ በገበያ ላይ ዋጋው እንዳያሽቆለቁል ለማድረግ እንደተዘጋጁ ገልፀዋል - በታህሳስ ወር።
በእርግጥ እንደዚህ ቢያስቡ አይገርምም። የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለስልጣን መረጃዎች ሲታዩ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚመረተው ስንዴ በተለይ ባለፉት ስድስት አመታት በእጅጉ ጨምሯል። በ2001 ዓ.ም የስንዴ ምርት 25 ሚሊዮን ኩንታል፤ በ2004 ዓ.ም ደግሞ 29 ሚሊዮን ኩንታል እንደነበር ይገልፃል የባለስልጣኑ መረጃ። አምና በከፍተኛ የምርት እድገት 34 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ እንደተሰበሰበ አመታዊው የባለስልጣኑ ሪፖርት ያመለክታል። ዘንድሮ ደግሞ አርባ ሚሊዮን ኩንታል።
ሪፖርቶቹ እውነተኛ ከሆኑ፣ የስንዴ ምርት በሁለት አመታት ውስጥ በ11 ሚሊዮን ኩንታል ጨምሯል ማለት ነው። የ45% እድገት ቀላል አይደለም፡፡ አስደናቂ ነው፡፡ “ምርት ተትረፈረፈ” ያስብላል፡፡
ግንቦት 20 በሚከበርበት እለት ደግሞ ተጨማሪ ትልቅ ስኬት ተበሰረ፡፡ ለተከታታይ አመታት በተመዘገበው የግብርና እድገት ዘንድሮ ኢትዮጵያ በእህል ምርት ራሷን ችላለች በማለት ጠ/ሚ ሃይለማርያም ደሳለኝ ተናግረዋል፡፡ ድንቅ ነው፡፡
የእህል ምርት እየጨመረ መምጣቱ አይካድም፡፡ ጥሩ ነው፡፡ “ኢትዮጵያ በእህል ምርት ራሷን ችላለች” ብሎ መናገር ግን ሌላ ነገር ነው፡፡ ያለ መንግስት ድጐማ ኑሯቸውን መቀጠል የማይችሉ 6.5 ሚሊዮን ችግረኛ የገጠር ነዋሪዎች አሉ፡፡ ያለ ውጭ እርዳታ በህይወት መቆየት የማይችሉ 6.5 ሚሊዮን ረሃብተኞች መኖራቸውን ደግሞ ዩኤን ገልጿል፡፡ በድምሩ 13 ሚሊዮን
ተረጂዎች ያሉባት አገር “በእህል ምርት ራሷን ችላለች” ሲባል ምን ትርጉም አለው?
የመንግስት ብስራት ግን በዚህ አላቆመም፡፡ የስንዴ ምርት በእጅጉ እያደገ መሆኑን በመጥቀስ፤ “ኤክስፖርት ይደረጋል” በማለት የመንግስት ባለስልጣናት ሲናገሩ ከርመዋል፡፡ የሆይ ሆይታው ተከፋይ የሆኑት የእህል ንግድ ድርጅት የስራ ሃላፊዎች፤ ከዚህ “ብስራት እና “ስኬት” የተለየ ነገር አልተናገሩም፡፡ እንዲያውም የተወሰነ ያህል ቁጥብነት አሳይተዋል፡፡ ባለፈው አመት ምን እንደሰሩና ለዘንድሮ ምን እንዳቀዱ የድርጅቱ የስራ ሃላፊዎች ሲዘረዝሩ እንመልከት፡፡
በ2005 ዓ.ም ወደ አምስት ሚሊዮን ኩንታል ገደማ ስንዴ በ4.5 ቢሊዮን ብር ከውጭ ሀገር በመግዛት ገበያውን ለማረጋጋት እንደተቻለ ለዋልታ የገለፁት ዋና ስራ አስኪያጁ አቶ ብርሃኑ ሃይሉ፤ ዘንድሮ በቂ ስንዴ ስለተመረተ ከውጭ አገር ገዝተን አናስመጣም አላሉም፡፡ ግን እንደሌላው ጊዜ በፍጥነት ስንዴ ለመግዛትም ውሳኔ አላስተላለፉም።    
ከ2005 ዓ.ም ጋር ሲነፃፀር በ2006 ዓ.ም የሚሰበሰበው የስንዴ ምርት በ4 ሚሊዮን ኩንታል እንደሚበልጥ የተናገሩት የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ፤ የስንዴ እጥረትንና የዋጋ ንረትን ለማቃለል ታስቦ ከውጭ እየተገዛ የሚመጣው ስንዴ ዘንድሮ በግማሽ እንደሚቀንስ ገልፀዋል፡፡ አምና ከውጭ ተገዝቶ የመጣው ስንዴ ከ5 ኩንታል በላይ ስለሆነ ዘንድሮ 2.5 ሚሊዮን ኩንታል ብቻ ይሆናል ማለት ነው፡፡
 “ዘንድሮ ከውጭ ገበያ የሚገዛው ስንዴ በግማሽ እንደሚቀነስ ነው ዋና ስራ አስኪያጁ ያመላከቱት” ብሏል ፋናቢሲ በታህሳስ 28 ቀን ዘገባው።
የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለስልጣን መረጃ፣ የመንግስት ባለስልጣናት ሆይሆይታ እና የእህል ንግድ ድርጅት ሃላፊዎች ውሳኔ ውሎ አድሮ መጨረሻው አላማረም፡፡
ገና የካቲት ወር ላይ ነው በስንዴ እጥረት የአገሪቱ ዳቦ ቤቶች መቸገር የጀመሩት፡፡ እንደታሰበው በ2.5 ሚሊዮን ኩንታል ግዢ ብቻ የስንዴ እጥረትን ማቃለል እንደማይቻል በግልጽ እየታየ የመጣው፤ ስራ ፈትተው በራቸውን የሚዘጉ ዳቦ ቦቶቹ ሲበራከቱ ነው፡፡
ለዚህም ነው የኋላ ኋላ አራት ሚሊዮን ኩንታል ለመግዛት የተወሰነው፡፡ ለነገሩ ቀደም ሲል የታሰበው 2.5 ሚ ኩንታል ስንዴ፤ ቶሎ ተገዝቶ አልመጣም። ለጊዜው በቂ ስንዴ ተመርቷል ስለተባለ ከውጭ አገር ገዝቶ ማስመጣት የሚያስቸኩል ጉዳይ አልሆነባቸውም፡፡
አሁን እንደምታዩት፤ የስንዴ እጥረት አፍጥጦ ወጥቷል፡፡ የመንግስት እና የእህል ንግድ ድርጅት ሆይሆይታ በመጨረሻ “ዳቦ አልቋል” ወደሚል ችግር አደረሰን፡፡  ነገር ግን የመንግስት ባለስልጣናትም ሆኑ የድርጅቱ ሃላፊዎች በተሳሳተ ግምት የስንዴ እጥረት እንደፈጠሩና ጥፋት እንደሰሩ አምነው አይቀበሉም፡፡
“የስንዴ እጥረት ተፈጠረ፤ ዱቄት ጠፋ፣ ዳቦ አለቀ” የሚል ቅሬታ ሲቀርብባቸው፤ “የአቅርቦት እጥረት የለም፤ ችግሩ የስርጭት ነው” የምትል የተለመደች ምላሽ ይሰጣሉ፡፡
የስርጭት ችግርምኮ የነሱ ጥፋት ነው፡፡ ግን ይሄንን ለማሰብ ጊዜ የላቸውም። በወሬ ብቻ የስንዴ እጥረትን የሚያስወግዱ ስለሚመስላቸው፤ ሌላ ነገር አይታያቸውም፡፡ “የአቅርቦት እጥረት የለም” የሚል ወሬ አላዋጣ ሲል ነው፤ የተስፋ ቃል መናገር የሚጀምሩት፡፡ “አይዟችሁ፡፡ ከሳምንት በኋላ ስንዴው ጅቡቲ ይደርሳል” በማለት በተስፋ እንድንጠብቅ ሰሞኑን ነግረውናል፡፡

በፍ/ቤት የመከላከያ ምስክሮች እየተደመጡ ነው
የረመዳን ፆም ዛሬ ወይም ነገ ይጀመራል

ከአወሊያ ት/ቤትና ከእስልምና ምክር ቤት ምርጫ ጋር ተያይዞ የተጀመረው ተቃውሞ ያዝ ለቀቅ እያለ አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ በየሳምንቱ አርብ ከጁምአ ፀሎት በኋላ የተለያዩ መፈክሮችን በማንገብ የታሰሩ የኮሚቴ አባላት እንዲፈቱ ጥያቄ ይቀርባል፡፡
በአወሊያ ት/ቤት መነሻነት “ድምፃችን ይሰማ” በሚል ከተፈጠረው መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ጋር በተያያዘ በእነ አቡበከር መሃመድ መዝገብ ስር 18 ግለሰቦች በሽብር ወንጀል ተከሰው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ሲሆን የመከላከያ ምስክሮቻቸውን ለፍ/ቤት እያስደመጡ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ቀደም ሲል በተከታታይ ሲካሄድ የነበረው የተቃውሞ ድምፅ የማሰማት ስነ-ስርአት “የእፎይታ ጊዜ” በሚል ለ4 ወራት ከተቋረጠ በኋላ፣ በድጋሚ የተጀመረው መጋቢት 19 ቀን 2006 ዓ.ም ነበር - በታላቁ አንዋር መስጂድ ከአርብ የጁምአ ስግደት በኋላ በተደረገ ተቃውሞ፡፡ በእለቱ ከፀሎትና ስግደት በኋላ ሁሉም በተመሳሳይ ደቂቃ ነጭ ሪቫን በማውለብለብ “አሜን! አሜን! አሜን!” የሚል መፈክር ያሰሙ ሲሆን ፖሊሶች ዳር ቆመው ጉዳዩን ሲከታተሉ ነበር፡፡
በቀጣዩቹ ሳምንታትም በማህበራዊ ድረ-ገፆች በሚተላለፉ መልእክቶች አማካይነት በታላቁ አንዋር መስጂድ፣ በፒያሳው ኑር መስጂድና በኒ መስጂድ ተመሳሳይ ተቃውሞዎች ሲቀርቡ የሰነበተ ሲሆን በክልል ባሉ አንዳንድ መስጂዶችም ተመሳሳይ ተቃውሞዎች ተደርገዋል፡፡
በተመረጡ መስጂዶች በየሳምንቱ አርብ በሚደረገው ሰላማዊ የተቃውሞ ድምፅ ማሰማት ላይ ተቃዋሚዎቹ “እኛም ኮሚቴው ነን፣ ፍትህ ለኮሚቴዎቻችን፤ ፍትህ ተነፍገን ትግላችን አይቆምም” የሚሉ መፈክሮችን በተደጋጋሚ ሲያስተጋቡ ቆይተዋል፡፡
ሁለት እጅን ከፍ አድርጎ በማጣመር የመታሰር ምልክትን ማሳየት፣ ነጭ ሪቫንን ማውለብለብ የመሳሰሉ ትዕይንቶችንም ለተቃውሞ መግለጫነት ተጠቅመውበታል፡፡
ተቃውሞው በሃገር ቤት ብቻ አልተወሰነም፡፡ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞችም የተለያዩ ተቃውሞዎችን አድርገዋል፡፡ ሚያዚያ 13 ቀን 2006 ዓ.ም በዋሽንግተን ዲሲ፣ የኮሚቴዎቹን መታሰር በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ የተደረገ ሲሆን በሌሎች የተለያዩ ቀናትም በደቡብ አፍሪካ እንዲሁም በለንደንና በኖርዌይ ዳያስፖራዎች ተመሳሳይ ዓላማ ያለው ሰላማዊ ሰልፎችን ማድረጋቸው ታውቋል፡፡
“ድምፃችን ይሰማ” የተሰኘው ድረ-ገፅ ሰ፣ኑን በለቀቀው መረጃ፤“አዳማ ከተማ በግራፊቲ አሸብርቃ አደረች” ሲል ባወጣው ፅሁፍበከተማዋ የተለያዩ ቦታዎች ተቃውሞውን የሚያስተጋቡ መልዕክቶች በየግድግዳዎቹ ላይ መለጠፋቸውን አመልክቷል፡፡ በድረ-ገፁ እንደተጠቀሰው፤ “ሙስሊሙን በማሰር ትግሉን ማስቆም አይቻልም”፣ “ኮሚቴው ይፈታ”፣ “ትግላችን ይቀጥላል”፣ “መንግስት ከዲናችን ላይ እጁን ያንሳ”፣ “በደማችን ይከብራል ዲናችን” የሚሉና ሌሎች መልዕክቶች ይገኙበታል፡፡
በአማርኛ፣ በትግርኛና በኦሮምኛ ቋንቋዎች የኮሚቴ አባላቱን የፍርድ ቤት ውሎ ጨምሮ ተያያዥ መረጃዎችን የሚለቀው “ድምፃችን ይሰማ” ድረ-ገፅ፤ ያለፉት ሁለት የረመዳን ወቅቶች በሰላማዊ ትግል ያለፉና በርካታ ሴራዎች የከሸፉበት እንደሆኑ ጠቅሶ፤ ከቀናት በኋላ በሚጀመረው የረመዳን ወርም ትግሉ ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያድግ አስታውቋል፡፡
“በረመዳን በሁሉም ጁምአዎችና በተመረጡ ቀናት ውስጥም ልዩ መሰናዶዎች ይኖራሉ” የሚለው ድረ - ገፁ፤ “ረመዳንና ተሃድሶ” በሚል ተከታታይ ፕሮግራም ህዝብ አሳታፊ ስራዎች እንደሚከናወኑ ጠቁሟል፡፡
ሰሞኑንም “ለረመዳን እንደርደር” በሚል መሪ ቃል በአወሊያ፣ በኮልፌ እፎይታ እና በኮልፌ አቅሳ መስጂዶች የፅዳት ዘመቻ መከናወኑን በፎቶግራፎች አስደግፎ አውጥቷል፡፡
በሌላ በኩል ታላቁ የረመዳን ፆም ዛሬ ወይም በነገው እለት እንደሚጀመር የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት አስታውቋል፡፡ መጀመርያ ላይ ከእንቅስቃሴው ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ 28 ግለሰቦች በሽብር መከሰሳቸው የሚታወስ ሲሆን አስሩ መከላከል ሳያስፈልጋቸው ፍርድ ቤት በነፃ እንደለቀቃቸው ይታወሳል፡፡ አስራ ስምንቱ ተከላከሉ በተባሉት መሰረት፤ ካለፉት ሳምንታት ጀምሮ የመከላከያ ምስክሮቻቸውን እያሰሙ እንደሆነም ይታወቃል፡፡
የኢፌዲሪ የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር ዶ/ር ሽፈራው ተ/ማርያም በየሳምንቱ አርብ ስለሚካሄደው ተቃውሞ መረጃው እንደሌላቸው ገልፀው ዝርዝር መረጃው ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እቅድ አፈፃፀም ጋር እንደሚሰጡ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡        

Published in ዜና

ትልቁ የሕንድ ሥጋ አቀናባሪ፣ የቀዘቀዙ ምግቦች አዘጋጅና ኤክስፖርተር አላና ግሩፕ (Allana Group) በ20 ሚሊዮን ዶላር (በ400 ሚሊዮን ብር ገደማ) ካፒታል፣ በኢትዮጵያ ሶማሌና በኦሮሚያ ዞኖች፣ ሥጋ ለማቀነባበርና ኤክስፖርት ለማድረግ መስማማቱ ተገለፀ፡፡  ኩባንያው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በኦሮሚያ ክልል በዝዋይ ከተማ አካባቢ በሰጠው 75 ሄክታር የኢንቨስትመንት መሬት ላይ የንግድ ምርት ለመጀመር አቅዷል፡፡
ሕንዳዊው ኢንቨስተርና የኩባንያው ኃላፊ ሚ/ር አማን አርዘካሃን፣ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የሥጋ ማቀነባበሪያና ኤክስፖርት ማድረጊያ ተቋም ለማቋቋም፣ ከአገር በቀሉ የዲዛይነሮችና አማካሪዎች ድርጅት ከኢቲጂ ጋር በኢንዱስትሪ ሚ/ር ተፈራርመዋል፡፡ በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት ሚ/ር ካዛን፣ መቀመጫው ሕንድ የሆነው አላና ግሩፕ፣ በኢትዮጵያ የቀንድ ከብት ሀብት ላይ እሴት ለመጨመር ይጥራል ሲሉ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የሕንድ አምባሳደር ሚ/ር ሳንዳይ ቨርማ፣ በኢትዮጵያ 5 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት ያደረጉትን የሕንድ ኩባያዎች ፈለግ ተከትሎ አላና ኢትዮጵያ መግባቱ በኢኮኖሚው ላይ የበለጠ እሴት እንደሚጨምር ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል፡፡  

Published in ዜና

አልሸባብ ፅንፈኛ ድርጅት የሆነው ኢትዮጵያ ወደ ሶማሊያ ጦር ሰራዊት በማዝመቷ ነው በማለት ኒው አፍሪካን መጽሔት የዘገበ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ የአልሸባብ ታጣቂዎች አፍጋኒስታን ሄደው ስልጠና የወሰዱት ገና ድሮ ነው በማለት ዘገባውን አጣጣለ፡፡
አልሸባብ በዩጋንዳ እና በኬኒያ በፈፀማቸው ጥቃቶች ሳቢያ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ውስጥ ስጋት መፍጠሩን በመጥቀስ ነው መጽሔቱ አልሸባብን የሚመለከት ሰፊ ዘገባ ያቀረበው፡፡
ዜጐች በሄዱበት ሁሉ በፍተሻ መከራቸውን እያዩ እንደሆነ መጽሔቱ ገልፆ፤ በኬኒያ እና በዛንዚባር የቱሪዝም ገቢ ክፉኛ አሽቆልቁሏል፤ የኬኒያ መንግስት የመከላከያ በጀቱን ለመጨመር ተገዷል፡፡
አልሸባብ ወደ አክራሪነት የተለወጠው፤ በ2006 የኢትዮጵያ መከላከያ ሀይል በአሜሪካ ድጋፍ ወደ ሶማሊያ  በመዝመቱ ነው ሲልም መጽሔቱ ኢትዮጵያን ተጠያቂ አድርጓል፡፡ በመጽሔቱ የቀረበው ውንጀላ መሰረተ ቢስ ነው ሲል ያጣጣለው የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ፤ ኢትዮጵያ አልሸባብን አዳከመች እንጂ ወደ አክራሪነት እንዲለወጥ አላደረገችም በማለት ሰፊ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ እንዲህ አይነቱ ውንጀላ በተደጋጋሚ የሚሰነዘር መሆኑን ሚኒስቴሩ ጠቅሶ፤ ነገር ግን ምንም አይነት ማስረጃ የማይቀርብበት መሰረተ ቢስ ውንጀላ ነው ብሏል፡፡
በሶማሊያ እየገነነ የነበረው የእስልምና ፍርድ ቤቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጦር በመመታቱ አይደለም አልሸባብ ያቆጠቆጠው፡፡ እንዲያውም የፍርድ ቤቶች ምክር ቤት ሶማሊያ ውስጥ እየተንቀሳቀሰ በነበረበት ወቅትና ከዚያ በፊት ወደ አፍጋኒስታን ለስልጠና ተልከው በነበሩ ቡድኖች ናቸው አልሸባብን የመሰረቱት ብሏል ሚኒስቴሩ፡፡
የእስልምና ፍርድ ቤቶች ህብረት ኢትዮጵያ ላይ ጦርነት አውጆ እንደነበር ሚኒስቴሩ አስታውሶ፤ ያንን ጥቃት ለመከላከል የተወሰደው ወታደራዊ እርምጃ ተገቢ ነበር ብሏል፡፡
ወታደራዊ እርምጃ የወሰድነውም፤ አለም አቀፍ ህጐችን በማይጥስ መንገድና ከሶማሊያ የሽግግር መንግስት በተደረገልን ግብዣ ነው ብሏል - ሚኒስቴሩ፡፡  የኢትዮጵያ ጦር ሶስት አመት ሶማሊያ ውስጥ በቆየበት ወቅት ምንም አይነት ድጋፍ ከአሜሪካን እንዳልተሰጠውም ጠቅሷል፡፡

Published in ዜና

የቀረቡባቸውን ክሶች አልፈፀምንም ሲሉ ክደው ተከራክረዋል

የቀድሞ የገቢዎችና ጉምሩክ ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታና ምክትላቸው አቶ ገ/ዋህድ ወ/ጊዮርጊስ የቀረበባቸውን የሙስና ክስ ክደው የተከራከሩ ሲሆን ፍ/ቤቱ የአቃቤ ህግን ምስክሮች ለማድመጥ ከሃምሌ 1 እስከ 17 ያሉትን ቀናት በቀጠሮነት ይዟል፡፡
ባለፈው ረቡዕ ከፍተኛ ፍ/ቤት ቀርበው የእምነት ክህደት ቃላቸውን የሰጡት አቶ መላኩ ፈንታ፤ በሁለት መዝገቦች የቀረቡባቸውን 11 ክሶች ሲክዱ ምክትላቸው አቶ ገ/ዋህድ ወ/ጊዮርጊስ የቀረቡባቸውን 22 ክሶች አልፈፀምንም ሲሉ ክደው ተከራክረዋል፡፡
አቶ መላኩ ፈንታ ላይ ከቀረቡት ክሶች መካከል፣ “ከተሰጣቸው ስልጣን በላይ በመሆን ክሶችን በማዘጋትና ሊከሰሱ የሚገባቸውን ነጋዴዎች እንዳይከሰሱ በማድረግ የመንግስትን ስራ በማያመች አኳኋን መምራት” የሚሉት የሚገኙበት ሲሆን አቶ መላኩ በእለቱ በሰጡት የእምነት ክህደት ቃል የተባሉትን ድርጊቶች እንዳልፈፀሙ ለፍ/ቤቱ ተናግረዋል፡፡
ሁለተኛ ተከሳሽ አቶ ገ/ዋህድ ወ/ጊዮርጊስ በበኩላቸው፤ የቀረቡባቸውን 22 ክሶች ክደው የተከራከሩ ሲሆን በተለየ በቤታቸው በተገኘ ስለተባለው የጦር መሣሪያ ባለቤታቸው ኮ/ል ሃይማኖት ተስፋዬ ታጋይ በመሆናቸውና እርሳቸውም የደንብ ማስከበር ሃላፊ ሆነው ሲሰሩ ያገኙት እንደሆነ በመጥቀስ ከወንጀል ሊቆጠርብኝ አይገባም ሲሉ ተከራክረዋል፡፡
የመንግስትን ስራ ያለ አግባብ መምራት ከሚለው ጋር በተያያዘ የቀረቡባቸውን ክሶችም ሆነ ምንጩ ያልታወቀ ገንዘብና ሃብት ይዞ መገኘት በሚል የቀረቡባቸውን ክሶች አቶ ገ/ዋህድ ክደው ተከራክረዋል፡፡
ቀደም ሲል በመዝገቦቹ የተጠቀሱ ከ40 በላይ ተከሳሾች የእምነት ክህደት ቃላቸውን በጠበቆቻቸው አማካይነት የሰጡ ሲሆን የአቶ መላኩና ገ/ዋህድ ተነጥሎ ሊቀርብ የቻለው ከጠበቆቻችን ጋር ተማክረን መልስ እንስጥ በማለታቸው እንደሆነ ይታወሳል፡፡
ተከሳሾቹ የቀረበባቸውን ክስ ክደው መከራከራቸውን ተከትሎ የፌደራል የስነ ምግርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አቃቤ ህግ ምስክሮቹን ለማሰማት እንዲፈቀድለት በጠየቀው መሠረት፣ ፍ/ቤቱ 17 ተከታታይ ቀናትን መርጦ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡  

Published in ዜና

“የሠራተኛ ማህበራት መሪዎች ከሥራ ይባረራሉ ወይም ከሰራተኛው ጋር እንዳይወያዩ አሰሪዎች የሥራ ጫና ያበዙባቸዋል”

የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማካ) በ16ኛ መደበኛ የጠቅላይ ም/ቤት ጉባኤ 550 አባላት ተሳትፈው አዲስ የሥራ አስፈጻሚና የኦዲት ኮሚቴ አባላት መረጡ፡፡
ኢሠማኮ ትናንት ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ያለፉትን ሁለት ዓመታት የሥራ አፈፃፀምና የኦዲት ሪፖርት ተወያይቶባቸው ያፀደቀ ሲሆን፣ ለመጪዎቹ አምስት ዓመታት የሚያገለግሉ 10 የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴና ሦስት የኦዲት ኮሚቴ አባላት መርጧል፡፡
ባለፈው ታኅሣሥ ወር ኢሠማኮ ለጠቅላይ ሚ/ሩ ያቀረባቸው 21 ጥያቄዎች ተቀባይነት በማግኘታቸው፣ ችግሮቹን ተከታትሎ የሚፈታ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየሰራ መሆኑን የጠቆሙት የኢሠማኮ ዋና ጸሐፊ አቶ መስፍን ስለሺ፣ ችግሮቹ በአንድ ጊዜ የሚፈቱ ስላልሆነ ጠቅላይ ሚ/ሩ በየ6 ወሩ እየተገናኘን እንደምንወያይባቸው ቃል ገብተውልናል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሠራተኞች በርካታ ችግሮች ቢኖሩባቸውም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቀረብናቸው 21 ችግሮች ዋነኞቹ በማኅበር የመደራጀትና የህብረት ድርድር አድርጎ የሰራተኛውን ጥቅም ማስከበር ቢሆንም አሰሪዎች ግን ሰራተኛው ማኅበር እንዲያቋቁምና ድርድር ማድረግ አይፈልጉም፡፡ የሰራተኞችን ችግሮች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅርበን ችግሮቹን የሚፈታ ኮሚቴ ከተቋቋመ ወዲህ መሻሻሎች ቢኖሩም በአጥጋቢ ሁኔታ እየተፈቱ ነው ማለት አያስችልም ብለዋል ዋና ጸሐፊው፡፡
አሰሪዎች፤ ሰራተኛው ከተደራጀ የመብት ጥያቄ ያነሳብናል በማለት እንዲደራጅ አይፈልጉም። ተደራጅቶና በማኅበራዊ ጉዳይ ሚ/ር እውቅና አግኝቶ ሲመጣ፣ የሰራተኛ ማኅበራት መሪዎችን በሙሉ ከሥራ ያባርራሉ ወይም የማኅበሩ አመራሮች ከሠራተኞቹ ጋር ተገናኝተው እንዳይወያዩ የሥራ ጫና ያበዙባቸዋል ያሉት የኢሠማኮ ም/ፕሬዚዳንት አቶ ዘነበ ከበደ፣ በማኅበር የመደራጀት ዋና ትርጉሙ በህብረት ስምምነቱ መሰረት አሰሪዎች ሰራተኛው የሚገባውን ጥቅማ ጥቅም እንዲሰጡ ግፊት ማድረግ ነው ብለዋል፡፡ ድርጅት የሚቋቋመው ለትርፍ እንጂ ለጽድቅ አይደለም፡፡
ሠራተኛው ስለጥቅሙ ከአሰሪው ጋር ተደራድሮ የኢንዱስትሪ ሰላምና ምቹ የሥራ ሁኔታ ሲፈጠር፣ ድርጅቱ አትራፊ ይሆናል፡፡ መንግሥትም የተሻለ ታክስ ያገኛል፡፡ ሠራተኛውም ቦነስ ያገኛል። ድርጅቱም ይጠቀማል፡፡ አሰሪዎች ግን ይህን አይፈልጉም፡፡ የሰራተኛን ማኅበር እንደጨቅጫቃ ስለሚቆጥሩ ሰራተኞች እንዲደራጁ አይፈልጉም ብለዋል ም/ፕሬዚዳንቱ፡፡  

Published in ዜና

የሸራተን ሠራተኛ ማህበርና ማኔጅመንቱ ለድርድር እንዲቀርቡ በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሰሪና ሰራተኛ ወሳኝ ቦርድ ባለፈው ማክሰኞ የወሰነ ሲሆን፤ የአዲስ አበባ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ አደራዳሪ እንዲመደብ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
የሸራተን ሆቴል ጠበቃ አቶ ተካ አስፋው፤ ክሱ እንዲሰረዝና ያለ አደራዳሪ ራሳቸው እንዲደራደሩ ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡
ላለፉት 6 ወራት የሸራተን ሰራተኛ ማህበር ማኔጅመንቱ በህብረት ስምምነቱ ላይ እንዲደራደር ጥያቄ ሲያቀርብ ቢቆይም ማኔጅመንቱ ለድርድር ፈቃደኛ ባለመሆኑ፣ ለኢንዱስትሪ ፌዴሬሽን የእገዛ ጥያቄ ማቅረቡን እንዲሁም ጉዳዩ ከፌዴሬሽኑ አቅም በላይ በመሆኑ ለኢሰማኮ ደብዳቤ መፃፉንና ኢሰማኮ ለማኔጅመንቱ የአምስት ቀን ጊዜ መስጠቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ማኔጅመንቱ የተሰጠውን የአምስት ቀን የጊዜ ገደብ ከጨረሰ በኋላ የኢንዱስትሪ ፌዴሬሽኑ ለአሰሪና ሰራተኛ ወሳኝ ቦርድ ክስ መስርቶ፣ ባለፈው ማክሰኞ  የፌዴሬሽኑ ጠበቃ አቶ ሰኢድ ይመርና የማኔጅመንቱ ጠበቃ የቀድሞው የስፖርት ፌዴሬሽን ም/ፕሬዚዳንት አቶ ተካ አስፋው በተገኙበት ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡
ቦርዱ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ፤ አደራዳሪ እንዲመድብ ትዕዛዝ እንደሚያስተላልፍ ገልጿል፡፡
በጉዳዩ ላይ ፌዴሬሽኑ በአደራዳሪነት እንዲገባ የኢንዱስትሪ ፌዴሬሽኑ ጠበቃ አቶ ሰኢድ ይመር የጠየቁ ሲሆን የሸራተን ሆቴል ጠበቃ አቶ ተካ አስፋው ጥያቄውን ተቃውመውታል፡፡ “በጭራሽ መደረግ የለበትም፤ ፌዴሬሽኑ በአደራዳሪነት ገባ ማለት በእሳት ላይ ቤንዚን እንደማርከፍከፍ ይቆጠራል” ብለዋል - አቶ ተካ፡፡ የፌዴሬሽኑ ጠበቃ አቶ ሰኢድ በበኩላቸው፤ “በህግ አምላክ! ህጋዊ ሰውነት ያለውን ድርጅት በዚህ መልኩ መዝለፍ በህግ ያስቀጣዎታል” ሲሉ ምላሽ የሰጡ ሲሆን ቦርዱ አቶ ተካ ከንግግራቸውን እንዲታቀቡ አድርጓል፡፡
የሠራተኛ ማህበሩና ማኔጅመንቱ ለድርድር ቀርበው እስከ ሀምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም  የደረሱበትን ሁኔታ ለቦርዱ ሪፖርት እንዲያደርጉ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡
በእለቱ ጉዳዩን ለመከታተል ከመጡት በርካታ የሸራተን ሰራተኞች መካከል አብዛኞቹ እንደገለፁልን፤ ሰራተኞች ችግራቸውን በሚዲያ ከገለፁ በኋላ፣ ሥራ አድረው ጠዋት ወደ ቤት ለሚሄዱ ሰራተኞች የሚቀርበው ሰርቪስ (የትራንስፖርት አገልግሎት) የቆመ ሲሆን በህመም፣ በጋብቻና በዘመድ ሞት ምክንያት አስፈቅዶ የቀረ ሰው ሰርቪስ ቻርጅ አይከፈለውም ተብሎ በድርጅቱ ሰሌዳ ላይ እንደተለጠፈም ጠቁመዋል፡፡
“የኪችን ሰራተኛ 350 ብር፣ የላውንደሪ ሰራተኛ፣ 400 ብር፣ የጥበቃ ሰራተኛ 450 ብር፣ እንግዳ ተቀባይ 700 ብር፣ አስተናጋጅ 450 ብር ደሞዝ እያገኘ በችግር ምክንያት የቀረን ሰው ሰርቪስ ቻርጅ አንከፍልም ማለት አሳፋሪ ነው” ብለዋል ሰራተኞቹ፡፡ የኢንዱስትሪ ፌዴሬሽኑ ጠበቃ አቶ ሰኢድ ይመር በበኩላቸው፤ በሰራተኞቹ ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ አግባብ ባለመሆኑ ድርጅቱ ከዚህ ድርጊቱ እንዲታቀብ ለቦርዱ አቤቱታ አቅርበዋል፡፡
ሰራተኞቹም የተወሰደው እርምጃ በህብረት ስምምነቱ የሌለና አዲስ የመጣ በመሆኑ ድርጅቱ የወሰደውን እርምጃ በአሰሪና ሰራተኛ አዋጁ መሰረት እንዲያነሳ ጠይቀዋል፡፡
ስለቀጣዩ የማህበሩና ማኔጅመንቱ ድርድር የጠየቅናቸው የሰራተኛ ማህበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ዳዊት ሳሙኤል፤ ጉዳዩ በፍ/ቤት የተያዘ መሆኑን ጠቅሰው፤ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡  

Published in ዜና
Page 4 of 18