ጀምስ ጆይስ (1882-1941)
ይሄ አየርላንዳዊ የሥነ-ፅሁፍ ሰው ከ20ኛው ክፍለ ዘመን እጅግ ዝነኛ ደራሲያን መካከል በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሽ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ1907 ዓ.ም “Chamber Music” የተሰኘ 36 ግጥሞችን ያካተተ መድበል ያሳተመ ሲሆን ከ 8 ዓመት በኋላ የመጀመሪያ ረዥም ልብ-ወለዱን ለህትመት አበቃ - “Dubliners” በሚል ርዕስ።
ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ እንደወረደ ስልት (stream of consciousness) የአተራረክ ዘይቤ በመጠቀም የፃፈውን “A portrait of the Artist as a young Man” የተሰኘ ልብ-ወለዱን አሳተመ፡፡ ጆይስ ከዚህ በመቀጠል ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያስገኘለትን “Ulysses” ነው ለንባብ  ያበቃው፡፡ የመጨረሻ ሥራው “Finnegan’s wake” በስነ-ፅሁፉ ዓለም ቀዝቃዛ አቀባበል በማግኘቱ ጆይስን ክፉኛ አስከፋው፡፡ አብዛኛውን ህይወቱን በገንዘብ ችግር ያሳለፈው ይሄ ዝነኛ ደራሲ፣ እስከ ዕድሜው የመጨረሻ ዓመታት ገደማ ድረስ ከስራው ምንም ገቢ አላገኘም ነበር፡፡
የጄምስ ጆይስ የአፃፃፍ ልማድ ከብዙዎቹ ደራስያን የተለየ ነበር፡፡ በቀን ምን ያህል ቃላት ወይም ገፆች እፅፋለሁ የሚለው ጉዳይ እምብዛም አሳስቦት አያውቅም፡፡ አንዲት ዓረፍተ ነገር ብቻ በመፃፍ ቀኑን  ሊያሳልፍ ይችላል፡፡ አንድ ወዳጁ “ደህና ፃፍኩ የምትለው ምን ያህል ስትፅፍ ነው?” ሲል ላቀረበለት ጥያቄ “ሦስት አረፍተ ነገሮች” በማለት መልሷል፡፡


ቭላድሚር ናቦኮቭ (1899-1977)
ትውልደ ሩሲያ አሜሪካዊ ደራሲው ቭላድሚር ናቦኮቭ፤ በረዥም ልብ-ወለድ ፀሃፊነቱ ይበልጥ ቢታወቅም ገጣሚና ሃያሲም ጭምር ነው፡፡ በከፍተኛ ፈጠራ የተሞላው አፃፃፉ እንደ 20ኛው ክፍለ ዘመን ታላቅ የሥነ-ፅሁፍ ሰውነቱ ከፍተኛ ተወዳጅነትን አትርፎለታል፡፡ ናቦኮቭ እ.ኤ.አ በ1955 ለንባብ በበቃው “Lolita” የተሰኘ ረዥም ልብ-ወለዱ ይበልጥ የሚታወቅ ሲሆን Pale Fire እና Ada የተሰኙ ተወዳጅነትን ያተረፉ ረዥም ልብ-ወለዶችንም ፅፏል፡፡ ሌሎች አያሌ ልብወለዶችን በእንግሊዝኛና በሩስያኛም የፃፈ ሲሆን፤ በርካታ የኢ-ልብወለድ ሥራዎችም አሉት፡፡
ቭላድሚር ናቦኮቭ የፅሁፍ ስራውን የሚያከናውነው ቁጭ ብሎ ወይም እንደ አንዳንድ ፀሃፍት ተጋድሞ ሳይሆን ቆሞ ነው፡፡ ለመፃፊያነት የሚጠቀመውም የተለመደውን ወረቀት አይደለም። በኢንዴክስ ካርዶች ነው የሚፅፈው፡፡ ይሄ ደግሞ ለትዕይንቶች ቅደም ተከተል ሳይጨነቅ እንዲፅፍ ነፃነት ይሰጠዋል፡፡ በኋላ የካርዶቹን ቅደም ተከተል እንደፈለገ ሊያስተካክል ይችላል፡፡ ደራሲው Ada የተሰኘውን ረዥም ልብ-ወለዱን ሲፅፍ ከ2ሺ በላይ ካርዶችን ተጠቅሟል፡፡


ጆይስ ካሮል ኦትስ
እ.ኤ.አ በ1938 የተወለደችው አሜሪካዊቷ ደራሲ ኦትነስ፤ በተለያዩ ዘውጎች በመፃፍ ትታወቃለች፡፡ አጭር ልብ-ወለዶች፣ ግጥሞች፣ ተውኔቶች፣ የሰሉ ወጎችና ረዥም ልብወለዶችን ትፅፋለች፡፡ ሶስት ተከታታይ (trilogy) ረዥም ልብ ወለዶችን የፃፈች ሲሆን በ1967 A Garden of Delights፣ በ1968 Expensive People እና በ1969 Them በሚል ለንባብ በቅተዋል፡፡
ከእነዚህም ውስጥ የመጨረሻው (Them ማለት ነው) በ1970 ዓ.ም የናሽናል ቡክ አዋርድ ተሸላሚ ሆኖላታል፡፡ ኦትስ ሌሎች በርካታ ሽልማቶችንም አሸንፋለች፡፡
የፈጠራ ሥራዋን የምትሰራበት የተወሰነ መደበኛ ሰዓት ባይኖራትም፣ ጠዋት ከቁርስ በፊት መፃፍ እንደምትመርጥ ትናገራለች፡፡ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የመጀመሪያ፣ ሁለተኛና ሶስተኛ ድግሪዋን የሰራችው ኦትስ፤ የበዩኒቨርሲቲ ፈጠራ አፃፃፍ የምታስተምር ስትሆን ክፍል ከመግባቷ በፊት ለአንድ ሰዓት ወይም ለ45 ደቂቃ ትፅፋለች፡፡ ክፍል በሌላት ጊዜ ደግሞ ለሰዓታት ስትፅፍ ቆይታ ቁርሷን ከሰዓት በኋላ በ8 ወይም በ9 ሰዓት ትመገባለች፡፡

Published in ጥበብ

      የእስራኤል ፕሬዚዳንት፣ ጠ/ሚንስትር፣ የገንዘብ ሚ/ር እና የኢኮኖሚ ሚ/ር በዝርዝሩ ውስጥ ተካተዋል
ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ታዋቂ ድምጻዊት ኢስተር ራዳ፣ ‘ዘ ጀሩሳሌም ፖስት’ ጋዜጣ የአመቱ የዓለማችን ተጽዕኖ ፈጣሪ አይሁዳውያን ብሎ ከመረጣቸው 50 ታዋቂ ግለሰቦች መካከል አንዷ ሆነች፡፡
በሶል፣ በአር ኤንድ ቢ እና በፋንክ ስልቶች የተቃኙና የኢትዮ-ጃዝ ቃና ያላቸው ሙዚቃዎችን የምትጫወተውና “የእስራኤል የሶል ሙዚቃ ንግስት” በመባል የምትጠራዋ ኢስተር ራዳ፣ በእስራኤል ብቻም ሳይሆን በመላ አለም በርካታ አድናቂዎችን ማፍራት የቻለች ድምጻዊት መሆኗን ‘ዘ ጀሩሳሌም ፖስት’ ባለፈው ሰኞ ይፋ ባደረገው መረጃ መስክሮላታል፡፡
ጋዜጣው ተስፋ ከሚጣልባቸውና ከፍተኛ ስኬት ካስመዘገቡ የዘመኑ ተጠቃሽ ቤተ እስራኤላውያን አርቲስቶች ተርታ ትሰለፋለች ያላት ይህቺ ድምጻዊት፣ በተለያዩ ጊዜያት በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ ስኬታማ የሙዚቃ ኮንሰርቶችን ማቅረቧንና፣ ኢትዮጵያዊ ቅኝት ያላቸውን ሙዚቃዎች እንደምትጫወትም ገልጧል፡፡
በሙዚቃው ዘርፍ ከፍተኛ ተወዳጅነትን ማፍራትና ለኤምቲቪ አውሮፓ የሙዚቃ ሽልማት እስከመታጨት የደረሰችው ኢስተር ራዳ፣ ‘ኪሮት’ እና ‘ስቲል ዎኪንግ’ን በመሳሰሉ ፊልሞች፣ ሙዚቃዊ ቲያትሮችና ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎች ላይ በተዋናይነት በመስራት ድንቅ የትወና ክህሎቷን አስመስክራለች፡፡
በተለያዩ የአለም ክፍሎች የሚኖሩ ፖለቲከኞች፣ ተመራማሪዎች፣ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች፣ ስራ ፈጣሪዎች፣ ቢሊየነሮች፣ አርቲስቶችና በሌሎች ሙያዎች ላይ ተሰማርተው ውጤታማ መሆን የቻሉ ግለሰቦችን በዘንድሮው የአመቱ 50 የአለማችን ተጽዕኖ ፈጣሪ አይሁዳውያን ዝርዝር ውስጥ ያካተተው ዘ ጀሩሳሌም ፖስት፤ ከእነዚህም ውስጥ ኢስተር ራዳን ጨምሮ 15 ያህሉ ሴቶች መሆናቸውን ይፋ አድርጓል፡፡
ካቻምና በእስራኤል ጠ/ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ፣ አምና ደግሞ በገንዘብ ሚንስትሩ የር ላፒድ ተይዞ የነበረውን የዚህ  ዝርዝር መሪነት፣ ዘንድሮ የአሜሪካ ትሬዠሪ ጸሃፊ የሆኑት ጃክ ሊው ተረክበውታል፡፡ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ቁልፍ ሚናን በሚጫወተው በዚህ ዘርፍ ውስጥ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ የሚገኙት እኒህ ሰው፣ በፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ አስተዳደር ውስጥ ተጽዕኖ መፍጠር የቻሉ ተሰሚ ሰው እንደሆኑ ጋዜጣው ዘግቧል፡፡
በተጽዕኖ ፈጣሪነት ሁለተኛውን ደረጃ የያዙት አሜሪካዊቷ ቤተ እስራኤላዊ ጃኔት የለን ሲሆኑ፣ የአሜሪካን ተቀማጭ ገንዘብ ተቋም እንዲመሩ በመመረጥ በአገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት ናቸው፡፡ እሳቸውን ተከትለው በዝርዝሩ የተካተቱት፣ ቤኒያሚን ኔታኒያሁ (የእስራኤል ጠ/ሚንስትር) እና ሽሞን ፔሬዝ (የእስራኤል ፕሬዚዳንት) ናቸው፡፡
አቪግዶር ሊበርማን (የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር)፣ የር ላፒድ (የእስራኤል የገንዘብ ሚንስትር) እና ናፋታሊ ቤኔትም (የእስራኤል የኢኮኖሚ ሚንስትር)፣ በዘንድሮው ተጽዕኖ ፈጣሪ ቤተ እስራኤላውያን ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱ ታዋቂና በአለም አቀፍ ደረጃ ተጽዕኖ መፍጠር የቻሉ ግለሰቦች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

Published in ጥበብ

        በቅርቡ ከንባብ የበቃውን የደራሲ ደሳለኝ ሥዩም “የታሰረ ፍትህ” ኢ-ልቦለድ መፅሃፍ አንብቤ ስጨርስ ወደ አዕምሮዬ የመጣው ጥያቄ፣ “ርዕሱ ለመፅሀፉ ጭብጥ አይከብደውምን?” የሚል ነው። መፅሀፉን የሚመጥን ርዕስ አልተሰጠውም የሚል አስተያየት አለኝ፡፡
የመፅሀፉ ጭብጥ በሀገር፣ በሕዝብ፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በጥበብና በማህበራዊ ሕይወት ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው፡፡ መተባበር እየጠፋ ስለ መምጣቱ፣ የሕግ ጥሰት ስለ መስፋፋቱ፣ ተስፋ አስቆራጭ ነገር ስለ መብዛቱ፣ አድርባይነት ስር ስለ መስደዱ፣ የሥነ ምግባር መላሸቅ ስለማየሉ ወዘተ…በመፅሐፉ ተዳስሷል፡፡
ደራሲው፤ ኢትዮጵያዊያን በአገር ጉዳይ ላይ የመተባበር ችግር እንዳለብን ምሳሌ እየጠቀሰ ያሳያል። በ1970 ዓ.ም የኢትዮ ሶማሊያ ጦርነት ሲካሄድ ኢህአፓ ደርግን መቃወሙ፤ በቅርቡም ኢሕአዴግ ወደ ሶማሊያ ሲዘምት ተቃዋሚ ፓርቲዎች አለመደገፋቸው፤ የህዳሴ ግድብ በኢሕአዴግ ዘመን መሰራቱን የሚቃወሙ ወገኖች ስለመኖራቸው፤ የግል ጋዜጦች የመንግሥት ጠላት ናቸው ብለው የሚያምኑ በርካታ ባለስልጣናት እንዳሉ… መፅሃፉ ማስረጃ እያቀረበ ያስቃኛል። የመተባበር ብቻ ሳይሆን አንዱ የሌላውን ሃሳብ፣ አመለካከት፣ ሃይማኖት፣ መብትና ነፃነት… ያለማክበር ችግርም በስፋት እንደሚስተዋል አስረግጦ ይገልጻል… ፀሃፊው፡፡
ዛሬ በአገራችን የሚታየው ሕግ የመጣስ ልማድ መነሻው የቆየ መሆኑን ለማሳየት ፀሐፊው የልጅ ኢያሱን ተግባር በምሳሌነት ያስታውሳል። ልጅ ኢያሱ በአዲስ አበባ የሰዓት እላፊ አዋጅ ካወጡ በኋላ ሕጉን በመጣስ፣ ከአራዳ ዘበኞች ጋር ሲታኮሱ ያደሩበት ታሪክ መመዝገቡን በመጠቆም። በንጉሱ ዘመን “ከፊውዳል ምክር ቤት” ወደ ፓርላማ ከተላኩት ረቂቅ አዋጆች ውስጥ ተቃውሞ ገጥሟቸው ሳይፀድቁ የሚቀሩ አዋጆች እንደነበሩ የሚገልፀው ፀሐፊው፤ ላለፉት 20 ዓመታት ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ፓርላማ ከላኳቸው ረቂቆች ውስጥ አንድም ውድቅ አለመደረጉን ይጠቁማል፡፡
“በራስህ ሳይሆን በእኔ ብቻ ተመራ፤ በሥራህ፣ በድካምና በጥረትህ መታወቅ ያለብህ አንተ ሳትሆን እኔ ነኝ” የሚለው አመለካከት የቱን ያህል እንደተንሰራፋ ለማሳየትም እንዲህ ይላል፡-
“ከእግዚአብሔር መስረቅ ብርቅ አልሆን ብሏል፡፡ የዕምነት ተቋማት አገልጋዮች ሲካሰሱና ሲዋቀሱ የምናስተውለው የእግዚአብሔር መሃሪነት በእነሱ ኢ - አመክኗዊነት ስለሚገራና እኛ ብቻ ነን ትክክል ስለሚሉ ብቻ አይደለም፡፡ ከዓለማዊ ስግብግብነታቸው የተነሳ ነው፡፡ ቢመነኩሱም፣ ቢቀስሱም፣ ቢፐሰትሩም መኪና መንዳት፣ ፎቅ ላይ መኖር፣ ጮማ መቁረጥ፣ እረፍት የሚነሳቸው ሕልም እየሆነባቸው ነው”
የዚህ ድምር ውጤት አስከፊና አስፈሪ እየሆነ መምጣቱን ለማስረገጥም በልጁ ላይ ተስፋ የቆረጠ አባት ታሪክ ቀርቧል፡፡ አባት የ11ኛ ክፍል ልጁ በፖሊስ ታስሯል፡፡ ልጁ የታሰረበትን ምክንያት ላለመናገር የቻለውን ያህል ጥረት ቢያደርግም የጐረቤቶቹና የወዳጆቹ ጉትገታ ሲበዛበት፤ ከጓደኞቹ ጋር ትምህርት ቤት ውስጥ ጋንጃ ሲያጨሱ በመያዛቸው ምክንያት እንደሆነ ይናገራል፡፡ ይህንን የሰማው የ5 ዓመት ወንድሙ፤ አባቱን “ጋንጃ ምንድነው” ብሎ ይጠይቀዋል፡፡ የአባት መልስ በተስፋ መቁረጥ ስሜት የተሞላ ነበር፤ “እባክህ አትጨቅጭቀኝ…ደርሰህ ለምትዘፈቅበት” አለው፡፡
በአገራችን የተንሰራፋው ሙሰኝነት፣ በየመሥሪያ ቤቱ የሚታየው ጉቦና የሥራ ልግመት፣ ሀገርና ሕዝብን አሳልፎ እስከመስጠት የሚደርሰው ህሊና ቢስነት፣ ሀገርን ለቆ የመሰደድ ፍላጐት መበራከት… ከላይ የተጠቀሰው ትልቅ ችግር ውጤት መሆኑን ይጠቁማል ፀሃፊው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ለአገርና ለሕዝብ የታተሩና የደከሙ ሰዎች አስታዋሽ አጥተው የትም ወድቀው መቅረታቸው ጥፋቱን እንዳባባሰው ይገልፃል - የአንድ አሳዛኝ አስተማሪን ታሪክ በመጥቀስ፡፡
ለጥቅም መቧደን ሌላኛው የአገሪቱ ችግር ነው። ዩኒቨርስቲዎች ስፖንሰር እየሆኑና የዩኒቨርስቲ መምህራን የአድናቆት ምስክርነት እየሰፈረባቸው የታተሙ ቀሽም የግጥም መፃሕፍትን ይተቻል - በተለይ ደግሞ አድናቆት ሰጪዎቹን፡፡ ካፌዎችን እያንቀጠቀጠ ስላለው ወጣት ትውልድ፣ ስለቺቺኒያ፣ ስለ ግብረሰዶማዊያን የሚያስቃኘው ፀሃፊው፤ በአገራችን እየተስፋፋ የመጣውን ግብረሰዶማዊነት በተመለከተ አንድ የፌደራል ፖሊስ ባልደረባ የሰጠውን አስተያየት ያቀርባል፡፡ “አሁን ወደድንም ጠላንም አሳፋሪነቱ ለዜጐች እንጂ ለሕግ (መንግሥት) አይመስልም” ይሄ አስተያየት የአገሪቱ ችግሮች እየተቀረፉ ሳይሆን እየተባባሱ መምጣታቸውን አመልካች ነው ብሏል ፀሐፊው፡፡
“የታሠረ ፍትሕ” በሥነ ጥበብ ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ፅሁፎችንም አካትቷል፡፡ ከ1900 ዓ.ም ጀምሮ ያለውን የኢትዮጵያ ሥነ-ፅሁፍም እንዲህ ይቃኘዋል፡፡ እስከ 1928 ዓ.ም በሚዘልቀው የመጀመሪያ ዘመን የሥነ ፅሁፍ ዋነኛ ዓላማው ተረት መንገር ይመስላል፡፡ ሁለተኛው ዘመን በጣሊያን ወረራ ወቅት ያለፈ ሲሆን ሥነጽሑፍ መንግስታትን (ሥርዓትን) የመደገፍም የመቃወም አቅም እንዳለው የታየበት ነው፡፡ ሦስተኛው ዘመን ከጣሊያን መባረር እስከ 1953 ዓ.ም መዝለቁን፤ አራተኛው ዘመን ከመንግሥቱ ንዋይ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ እስከ ደርግ ጅማሬ መቆጠሩን፤ አምስተኛው ወቅት ከ1966 እስከ 1983 ዓ.ም መዝለቁንና ስድስተኛው ከደርግ ውድቀት አሁን እስካለንበት ያለውን እንደሚያካትት በመጥቀስ በእያንዳንዱ ዘመን የተመዘገቡ አንኳር ተግባራትን ያስቃኛል፡፡
በገጽ 62 “አፄ ምኒልክ የአፄ ቴዎድሮስ ልጅ እንደመሆናቸው” የሚለው ሐረግ ደራሲው ሊል የፈለገውን ሁሉም አንባቢ በቀላሉ ሊረዳለት ስለማይችል፣ ልጅ የሚለውን ቃል ቢያንስ በትምህርተ ጥቅስ ውስጥ ማስቀመጥ ነበረበት፡፡ ከዚህ ሁሉ የሚሻለውና የሚቀለው ግን አፄ ምኒልክ በልጅነታቸው በአፄ ቴዎድሮስ ዘንድ የመኖር ዕድል ማግኘታቸውን መግለጽ ነበር፡፡
በመጽሐፉ ጐልተው ከሚታዩ ችግሮች በዋናነት የሚጠቀሰው ጠቅላላ ብያኔና ፍረጃው ነው፡፡ “ሀገሪቱ የጨካኞች፣ የግፈኞች እና የይሉኝታ ቢሶች ስትሆን ዓይናችን እያየ ይገኛል” (ገጽ 22) ”ወጣቶች ጥበብ እንደ ድራፍት አልጠማቸውም። ማወቅ እንደጫት ቅጠል አልናፈቃቸውም፡፡ በሮኬት ተኩስ ወደ ሰማይ ሳይሆን በወሲብ ቅንዝር ቁልቁል መስፈንጠር ያረካቸዋል፡፡” (ገጽ 68) “ንጹህ ምግብ ቤት ብርቅ እየሆነ ነው” (ገጽ 70) “ትውልዱ ሌላው ቀርቶ የመብትና ግዴታውን ልክ ከየት እስከ የት እንደሆነ አያውቅም” (ገጽ 85) “ስለ ጐንደር ቢዘፈን ከቴዎድሮስ ውጭ ሌላኛውን የጐንደር ገጽታ የሚያሳይ አይደለም፡፡ ስለ ጐጃም ቢዘፈን ከበላይ ውጭ ሌላኛውን ገጽታ የሚያሳይ አይደለም” (ገጽ 93) “ሀገሬው ዝም ማለትን መርጧል፡፡ ምርጫ መጣልህ ቢሉት የሚደነግጥበት ቀለብ የለውም። ሀገርህ በኢኮኖሚ ተመነደገች ቢሉት ለማድመጥ ጊዜም ፈቃደኝነትም የለውም” (ገጽ 118)
አፄ ምኒልክ ለአንዱ ታላቅ ጀግና፣ ለሌላው ታላቅ ጠላት የሆኑባት ሀገር ውስጥ የምንኖረው በዚህ ዓይነት የተሳከረ አስተሳሰብ ስለተነከርን አይደለምን? ሲልም ይሞግታል “የታሰረ ፍትህ” ደራሲ ደሳለኝ ስዩም፡፡ ከዚህ በተረፈ እናንተ ደሞ አንብባችሁ የራሳችሁን ፍርድ ሰጡ፡፡

Published in ጥበብ

     ገብርኤሉ ተረፈ ይባላል፤ ትውልድና እድገቱ ጎጃም ደጀን አካባቢ ነው፡፡ በለጋ ዕድሜው ወላጆቹን በሞት ያጣው ገብርኤሉ፤ ከልጅነቱ ጀምሮ ገንዘብ ሊያስገኙ የሚችሉ ነገሮችን እየሰራ በመሸጥ ራሱን እያገዘ ኖሯል፡፡ የጫማ መስፊያ ወስፌ በመስራት የራሱን ገቢ ማግኘት የጀመረው የ32 ዓመቱ ወጣት፤ ለሆቴሎች የማስታወቂያ ፅሁፍ በመፃፍና ስዕል በመሳል ወደ ፈጠራ ጥበብ ማደጉን ይናገራል፡፡ ትምህርቱን ከዘጠነኛ ክፍል በማቆም ወደ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ ለባለፀግነት ያበቁትን የተለያዩ የፈጠራ ስራዎች ሲሰራ የቆዩ ሲሆን በቅርቡም ሄሊኮፕተር መስራቱን ይገልፃል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከወጣቱ የፈጠራ ባለሙያ ገብርኤሉ ተረፈ ጋር በህይወቱ፣  በፈጠራ አጀማመሩ፣ በሰራት ሄሊኮፕተርና በቀጣይ እቅዱ ዙሪያ ተከታዩን  ቃለምልልስ አድርጋለች፡፡

የፈጠራ ስራ ፍላጎት ያደረብህ መቼ ነው?
ከልጅነቴ ጀምሮ ነገሮችን በአትኩሮት ማየትና መመራመር እወድ ነበር፡፡ በእርግጥ እናቴ ደሀ ስለነበረች ጠላ እየሸጠች ነበር የምታስተምረኝ፡፡ እኔም ሳንቲም የሚያወጡ ትንንሽ ነገሮችን እየሰራሁ እሸጥ ነበር፡፡
ለምሳሌ ምን ትሸጥ ነበር?
ለምሳሌ ሊስትሮዎች ጫማ የሚሰፉበትን የጫማ ወስፌ እየሰራሁ እሸጣለሁ፡፡ እናቴ ያኔ ጠላ ሸጣ በ15 ቀን የማታገኘውን ገንዘብ እኔ በቀን አገኝ ነበር። ከልጅነቴ ጀምሮ ስዕል መሳል አዳዲስ ነገሮችን መፍጠር እወዳለሁ፡፡ የጫማ ወስፌ ሰርቼ መሸጥ የጀመርኩት ገና የሁለተኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ ነበር። ከዚያ ከፍ ስል ስዕል ወደ መሳል ገባሁ። ስዕሉንም የገቢ ምንጭ አደረግሁት፡፡ በየሆቴሉ እየሄድኩ ግድግዳ ላይ ጥሩ ጥሩ ስዕሎችን መስራትና የሆቴል ማስታወቂዎችን መፃፍ ስራዬ ሆነ፡፡
ተወልደህ ያደግኸው ጎጃም ደጀን ውስጥ ነው፡፡ እንዴት ወደ አዲስ አበባ መጣህ?
ወደ አዲስ አበባ የመጣሁት በጣም ልጅ ሆኜ ከ20 ዓመት በፊት ነው፡፡ የመጣሁበትም ምክንያት እናቴ በመሞቷ ነው፡፡ አባቴ ህፃን ሆኜ በመሞቱ፣ እናቴ ነበረች የምታሳድገኝ፡፡ እሷ ስትሞት ሁሉንም ነገር ትቼ ወደዚህ መጣሁ፡፡ ከዚያም የሻይ ማፍያ ማሽኖችን መስራት ጀመርኩ፡፡ ያኔ የሻይ ማፍያ ማሽን በጣም አዋጪ ስለነበር፣ ገንዘብ ማግኘት ጀመርኩኝ። ቤትም መኪናም እስከ መግዛት ደርሻለሁ፡፡
ቀደም ብለህ እንደነገርከኝ በኑሮ ጫና ምክንያት ትምህርትህን ከዘጠነኛ ክፍል አቋርጠሃል፡፡ ቴክኒክና ሙያ ሳትማር ወይም ቴክኖሎጂ ነክ እውቀት ሳይኖርህ እንዴት የፈጠራ ስራ ላይ ልታተኩር ቻልክ?
በዚህ በፈጠራ ስራ ላይ ለምን ፍቅር እንዳደረብኝ ለራሴም ግልፅ አይደለም፤ ነገር ግን ነገሮች ወደ አዕምሮዬ መጥተው ሲታዩኝ ወዲያው ወደ ተግባር ለመቀየር እጣደፋለሁ፡፡ ወደ አእምሮዬ የመጣን የትኛውንም ምስል በድፍረት መሞከር እወዳለሁ፡፡ በጣም ድፍረት አለኝ፡፡ ለምሳሌ አንድን አውሮፕላን እሰራለሁ ብለሽ ስታስቢ፣ መጀመሪያ በምናብሽ (አዕምሮሽ) ትስይዋለሽ፡፡ ሁሉ ነገር አዕምሮሽ ውስጥ ነው የሚያልቀው፡፡ ከዚያ አዕምሮሽ ውስጥ ያለውን ስዕል ወደ እውነታ ትቀይሪያለሽ። ይህ ብዙ ፈተናዎች ሊኖሩት ይችላሉ፡፡ አዕምሮ ውስጥ ማብላላትን ይጠይቃል፡፡ ለእኔ የፈጠራ ስራ የምመሰጥበት ጉዳይ ነው፡፡ ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ ትምህርቴ ከዘጠነኛ ክፍል የዘለለ አይደለም፤ ነገር ግን ብዙ የፈጠራ ስራዎች ወደ አዕምሮዬ ይመጣሉ፡፡ እሰራቸዋለሁ፡፡
እስካሁን ምን ያህል የሻይ ማፍያ ማሽኖችን ሰርተህ ሸጠሃል?
ከአንድ ሺህ በላይ ይሆናሉ፡፡
አንድ የሻይ ማሽን ለመስራት ምን ያህል ጊዜ ይፈጅብሃል? ከምን ከምን ዓይነት ቁሳቁሶች ነው የምትሰራው?
የተለያዩ ታንከሮችን፣ የብረት ቱቦዎችን፣ ላሜራዎችንና መሰል ቁሳቁሶችን እጠቀማለሁ፡፡ አንድ የሻይ ማሽን ለመስራት ቢበዛ ሳምንትና ከዚያ በታች ነው የሚወስድብኝ፡፡ አንዱን ማሽን የዛሬ ዘጠኝ አመት አካባቢ ከ7-9 ሺህ ብር እሸጠው ነበር።
አሁንስ?
አሁን ስራው ስለደከመ የሻይ ማሽን አልሰራም። ስራው የደከመበት ምክንያት እዚህ አገር የፈጠራ ስራ ስትሰሪ የሚያበረታታሽ የለም፡፡ የሻይ ማሽን የሚሸጡ ሰዎች የአገር ውስጥ ማሽኖችን አትግዙ ይላሉ፡፡ በሌላ በኩል የሻይ ማሽን ነጋዴዎች ከውጭ የደከሙ ማሽኖች ያስገቡና ውጭያቸውን እየቀየሩና ቴክኒካቸውን እያደሱ፣ ከአገር ውስጡ የሻይ ማሽን ከፍ ባለ፣ ከውጭው ዝቅ ባለ ዋጋ በመሸጥ፣ አገር ውስጥ እየሰራን የምንሸጠውን ከጨዋታ ውጭ አደረጉን፡፡ በዚህ የተነሳ ስራውን ለመተው ተገድጃለሁ፡፡
አሁን በቋሚነት የምትሰራው ምንድነው?
በአሁኑ ወቅት ምንም በቋሚነት የምሰራው ስራ የለኝም፡፡ ነገር ግን በአዕምሮዬ ውስጥ ብዙ የፈጠራ ስራዎች ስላሉኝ የት፣   ልሂድ የትም እነዚያን ነገሮች እውን ማድረግ እፈልጋለሁ፡፡ የፈጠራ ክህሎቴንም የበለጠ የማሳደግ ህልም አለኝ፡፡
በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነችውን ሄሊኮፕተር ሰርተሃል፡፡ እስቲ ስለ ሄሊኮፕተሯ በአዕምሮህ መጠንሰስ ከዚያም እንዴት ወደ እውነታው እንዳመጣሃት ንገረኝ…
የሄሊኮፕተሯ ጉዳይ በሀሳብ ደረጃ በአዕምሮዬ ለረጅም ጊዜ አርግዣት የቆየች ናት፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ የአውሮፕላንና የሄሊኮፕተርን ጉዳይ አስብ ነበር። በትንሹ አምስት አመትና ከዚያ በላይ በአዕምሮዬ ውስጥ የተጠነሰሰ ጉዳይ ነው፡፡ ሄሊኮፕሯን በተግባር ለመስራት ግን አንድ አመት ነው የፈጀብኝ፡፡ ቅድም እንዳልኩሽ አንድ የፈጠራ ስራ ቀድሞ የሚያልቀው አዕምሮ ውስጥ ነው፡፡
ሄሊኮፕተሯን ለመስራት ምን ግብአቶች ተጠቀምክ?
ከብረታ ብረት ነው የሰራኋት፡፡ ከላይ የሚሽከረከረውን ነገር ከፋይበርግላስ፣ ኢንጂኗን ከሞተር ሳይክል ነው የሰራሁት፡፡ ምን አለፋሽ… ከወዳደቁ ነገሮች ነው የሰራኋት ማለት እችላለሁ። እርግጥ ኢንጂኑን በትክክል ለማምጣት የተለያዩ ሞተር ሳይክሎችን እየገዛሁ ስሞክርና ስጥል ቆይቻለሁ፡፡
ከሁሉም የገረመኝ የሰራሃት ሄሊኮፕተር በሻንጣ ተጣጥፋ መያዝ የምትችል መሆኑን ስሰማ ነው፡፡ ይሄ እውነት ነው?
አዎ! ትያዛለች፡፡ የአሰራሯ ሁኔታ ነው ተጣጥፋ እንድትያዝ የሚያደርጋት፡፡ በዚህም ከሌሎች ትለያለች።
ሄሊኮፕተሯ ስትበር አሳይተሃል?
በደንብ በርራለች፡፡ ይህንን ሳላረጋግጥማ ሄሊኮፕተር ናት ብዬ ለመናገርም አልደፍርም፡፡
ሄሊኮፕተሯን ለመጎብኘት የመጣነው በዚህ “የምርታማነት ማሻሻያ ማዕከል” ውስጥ ነው፡፡ በዚህ  ወርክሾፕ ውስጥ ለመስራት እንዴት ተፈቀደልህ?
ስራው አመቺ ቦታ ይፈልጋል፡፡ ይህ ማዕከል ደግሞ ለሥራው ጥሩ ቦታ ነው፡፡ ወደ ማዕከሉ ዳይሬክተር አቶ ገ/ኪዳን የመጣሁት በፈጠራ ስራ ላይ የሚተጉ ሰዎችን እንደሚያበረታቱ ስለማውቅ ነበር፡፡ ነገር ግን እሳቸው አልነበሩም፡፡ “የሉም” ሲባል እቅዴ ላይሳካ ነው በሚል አዝኜ ነበር፡፡ ሌላ ማንን እንደማናግር ለሰዎች ሳማክር፣ የማዕከሉን ምክትል ዳይሬክተር አቶ በረከትን ማናገር እንደምችል ተጠቆምኩኝ። አቶ ዳዊት የሚባሉ የማዕከሉ ሰራተኛ ናቸው አቶ በረከትን አናግር ያሉኝ። አናገርኳቸው። ከጠበቅሁት በላይ ተባባሪና ለፈጠራ ስራ ትልቅ አክብሮት ያላቸው ሆነው አገኘኋቸው። ወዲያው አስፈቀዱልኝ፡፡ በዚህ ማዕከል ወርክሾፕ ውስጥ ነው ሄሊኮፕተሯን የሰራኋት። በነገርሽ ላይ እስከዛሬ ድረስ እንደ አቶ በረከት አይነት ቅንና ተባባሪ ሰው አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡
አሁን ለምንድነው ሄሊኮፕተሯን የፈታታሀት?
ሞተሯ የሚነሳው ገመድ በመሳብ አሊያም እንደሞተር ሳይክል በመረገጥ ነበር፡፡ ይህ ሲሆን ሌላውን አካሏን እንዳይጐዳብኝና ጥራቷ እንዳይቀንስ በሚል ልክ እንደመኪና በቁልፍ እንድትነሳ ለማድረግ፣ እሱን ሞዲፍኬሽን በመስራት ላይ ነኝ። አሁን እሱም እየተሳካ ነው፤ ጥቂት ነገር ብቻ ነው የቀረኝ፡፡
በቅርቡ በይፋ ልታስመርቃት እንደሆነ ሰምቻለሁ። ትክክለኛ መረጃ ነው?
እውነት ነው፡፡ እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ በሁለትና በሶስት ሳምንት ውስጥ ህዝብ በተሰበሰበበት በይፋ አስመርቃታለሁ፡፡
በዓለም ላይ በየጊዜው በርካታ የፈጠራ ስራዎች ይሰራሉ፡፡ ከዚህ አንፃር ሄሊኮፕተር በመስራት ሰው በአፍሪካ የመጀመሪያው መሆንህን በምን አረጋገጥክ?
ኢንተርኔት ገብቼ ለመፈተሽ ሞክሬያለሁ፡፡ እስካሁን አንድ አሜሪካዊና አንድ ጃፓናዊ ናቸው የሰሩት፡፡ የጃፓኑ “ጊነስ ቡክ ኦፍ ሬከርድስ” ላይ ተመዝግቧል፡፡ በአፍሪካ ሄሊኮፕተር የሰራ ካለ ብዬ ብዙ ሰርች አድርጌያለሁ፤ የሰራ የለም፡፡ ለዚህ ነው እርግጠኛ ሆኜ የመጀመሪያው ነኝ ያልኩሽ፡፡
በአፍሪካ የመጀመሪያው ሄሊኮፕተር የሰራህ ሰው መሆንህን ስታስብ ምን ይሰማሃል?
ዋው! ልነግርሽ አልችልም፡፡ ለግል ዝናና ክብር አይደለም ይህን የምልሽ፣ እኛ ኢትዮጵያዊያን በሌላው ዓለም ፓስታ እንኳን መመገብ የማንችልና መስራት የማንሞክር ተደርገን ነው የምንታየው። በረሀብና በጦርነት ነው ስማችን ሲነሳ የኖረው። ይሄ በግሌ ይቆጨኛል፡፡ ሀበሾች ይህን ያህል መስራት የሚችል ጭንቅላት ባለቤት መሆናችንን ዓለም ቢያውቅ ደስ ይለኛል፡፡ በአትሌቲክሱ፣ በጠፈር ተመራማሪነት፣ በህክምና፣ በፈጠራና መሰል ዘርፎች ኢትዮጵያዊያን ትልቅ አቅም እንዳለን ዓለም እንዲያውቅ እፈልጋለሁ። ለዚህ አስተሳሰብ መለወጥ የበኩሌን አስተዋፅኦ ማበርከቴን ስገነዘብ በሃሴት እሞላለሁ፡፡ ደስ የሚል ስሜት ይሰማኛል፡፡ እኔ በትምህርቴ ገፍቼ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ባልማርም፤ ቴክኒክና ሙያ ባልከታተልም፣ እድሜ ለኢንተርኔት የማላውቀው ነገር የለም፡፡ አስተማሪዬ ኢንተርኔት ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ለአምስትና ለስድስት ሰዓት ኢንተርኔት ላይ ተመስጬ ቁጭ የምልበት ሰዓት ሁሉ አለ፡፡ ራሴን አስተምሬ ለዚህ ውጤት በመብቃቴም ሌላ የሚሰማኝ ተጨማሪ ደስታ አለ፡፡
በጠቀስካቸው የአሜሪካና ጃፓን ዜጎች የተሰሩት ሄሊኮፕተሮች አንተ ከሰራሃት ሄሊኮፕተር በምን ይለያሉ?
የጃፓኑ ሄሊኮፕተር አራት ፒስተን ኢንጂን ነው፤ ፎርስትሮክ ይባላል፡፡ በዚያ ላይ 80 የፈረስ ጉልበት ሀይል አለው፡፡ የአሜሪካኑ ደግሞ መጠኑ ትንሽ ሆኖ 40 የፈረስ ጉልበት ሀይል ሲኖረው ባለ አንድ ፒስተን ኢንጂን ነው፤ ፎርስትሮክ ይሁን ቱስትሮክ ግን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡
የእኔ ከእነሱ የሚለይበት እኔ የተጠቀምኩት ኢንጂን የሞተር ሳይክል ነው። ያመሀ የተባለ ሞተር ሳይክል ኢንጂን ሲሆን 250 ሲሲ ነው፡፡ እኛ አገር የፈረስ ጉልበት ምን ያህል እንደሆነ መለካት ባይቻልም ስገምት ግን ከ40 በላይ የፈረስ ጉልበት አለው ብዬ አምናለሁ፡፡ ከ42-45 የፈረስ ጉልበት ይሆናል ሀይሏ፡፡
የሄሊኮፕተሯን እሽክርክሪት ከፋይበር ግላስ የመስራት ሃሳብ እንዴት መጣልህ? ከዚያ በፊት የሞከርከው ሌላ ማቴሪያል ነበር?
ክንፉን ለመስራት ብዙ ዓይነት ማቴሪያል ተጠቅሜያለሁ:: ብዙ ብርም አውጥቻለሁ፤ ግን አልተሳካልኝም ነበር፡፡ ለምሳሌ “አቢቲ” የሚባል የእንጨት አይነት አለ፤ በጣም ውድ እንጨት ነው። ብዙ ጊዜ እየገዛሁ ሞክሬዋለሁ፤ ግን አልሆነም። ከሁሉም እሽክርክሪቱ በጣም ፈትኖኛል፡፡ መጨረሻ ላይ ሄሊኮፕተሯ እንድትነሳ ትልቁን ሚና የተጫወተው ፋይበር ግላሱ ነው፡፡ እንደምታዩት ፋይበር ግላሱ ስስ ይመስላል፤ በኬሚካል ሲጣበቅ ግን ለጥንካሬው ወደር የለውም፤ እናም ክንፉ ከፋይበር ግላስ ተሰርቶ ፈታኝነቱ አብቅቷል፡፡
አሜሪካዊው እና ጃፓናዊው ከሰሯቸው ሄሊኮፕተሮች ያንተ የምትሻልበት ነገር አለ?
አዎ! አንደኛ የእኔ ባለ አንድ ፒስተን ናት፡፡
ፒስተን ምን ማለት ነው?
ፒስተን ማለት የሄሊኮፕተሩ ማስነሻ ሀይል (እሳት የሚነሳበት ክፍል) ማለት ነው፡፡ አንድ ፒስተን ሁለት ፒስተን፣ ሶስት፣ አራት እያለ ይቀጥላል፡፡ የጃፓኑ ባለ አራት ፒስተን ነው ብየሻለሁ፡፡
የአሜሪካኑ ባለ አንድ ፒስተን ቢሆንም በጣም አነስተኛ ናት፤ በጭንቅላቱ ተሸክሟት ይሄዳል፡፡ የእኔ ባለ አንድ ፒስተን ናት፤ የራሷ ወንበር አላት፤ ቀበቶ አስረሽ መብረር ትችያለሽ፤ ስለዚህ የእኔ በብዙ መንገድ ትሻላለች፡፡
አንተ ራስህ በትክክል አብርረሃታል?
ምን መሰለሽ… የእኔ የኢንጂን ሲስተሙ የሄሊኮፕተር ሳይሆን የሞተር ሳይክል በመሆኑ ካንዴላ ሲስተም ነው፡፡ ኢንጂኑ በተፈጥሮው አንድ ክር ሲነቀል ሾርት ካደረገ ልትፈጠፈጪ ትችያለሽ፤ ስለዚህ እኔ በኢንጂኑ ስለማልተማመን አደጋ እንዳይመጣ ከመሬት አንድና ሁለት ሜትር ከፍታ ላይ እያስነሳሁ እሞክራታለሁ፡፡ እናም መነሳት መቻሏ ኢንጂኑ የሄሊኮፕተር ቢሆን ፐርፌክት መሆኑን ያረጋግጣል፡፡
ሁሉ ነገር ተሟልቶላት በብዛት ብትፈበረክ በዋናነት ለምን አገልግሎት ልትውል ትችላለች?
አሪፍ ጥያቄ አመጣሽ! ለመከላከያ ሰራዊት ትጠቅማለች፡፡ ለፖሊስም ታገለግላለች፡፡ ለምሳሌ ፖሊስ ሰርቆ ያመለጠን ሌባ፣ አደጋ አድርሶ የሚፈረጥጥን መኪናና አሽከርካሪ አሳዶ ለመያዝ ከፍተኛ ጥቅም ትሰጣለች፡፡
ሄሊኮፕተሯን ከወዳደቁ ብረቶችና መሰል ቁሳቁሶች እንደሰራሃት ነግረኸኛል፡፡ ግን በጠቅላላ ለስራው ከ200 ሺህ ብር በላይ ማውጣትህን ሰምቻለሁ፡፡ እንዴት ይህን ሁሉ ወጪ ልታወጣ ቻልክ?   
ለጥናት እሄዳለሁ፣ ስሄድ የነዳጅ እና ሌሎች ወጪዎች አወጣለሁ፡፡ ማሽን ቤት፣ ብየዳ ቤት ሄደሽ ታሰሪያለሽ፡፡ አንድ እቃ ገዝተሸ ስትሰሪ፣ ያ ይበላሽና በሌላ ትቀይሪዋለሽ፡፡ ለምሳሌ ተሽከርካሪ ክንፏን ለመስራት አቢቲ የሚባለውን ውድ እንጨት በተደጋጋሚ በውድ ዋጋ ገዝቻለሁ በመጨረሻ ግን  ፋይበርግላስ መቀየሬን ነግሬሻለሁ። የሚገጣጠሙትን ጥርሶች ገዝተሸ አንዱ ከአንዱ አልግባባ ሲል ሌላ ትቀይሪያለሽ፡፡ ሌላው ቀርቶ ኢንጂኑን በምፈልገው መጠን ለማምጣት የተለያዩ ሞተር ሳይክሎችን ለመግዛት ተገድጃለሁ፡፡ መጀመሪያ የገዛሁት ሞተር ሳይክል ኢንጂን አቅሙ ሲደክም ሌላ ገዛሁ፡፡ ከዚያም ሌላ ሞተር ሳይክል ገዛሁ፡፡ ሞተር ሳይክል እንደየአቅሙና ሁኔታው ከ7 ሺህ እስከ አስራ አምስት ሺህ ብር ይሸጣል፡፡ ይሄ ሁሉ ተደምሮ ከ200 ሺህ ብር በላይ ወጥቶበታል። በዚህ ላይ ደግሞ ጊዜና የጉልበቱን ነገር መዘንጋት የለብሽም፡፡
የፈጠራ ባለቤትነት መብት (Patent right) ማግኘትህን ሰምቻለሁ….
በትክክል! የፈጠራ ባለቤትነት መብት ከሳይንስና ቴክኖሎጂ አግኝቻለሁ፡፡ ተቃዋሚ ይኖር እንደሆነ በሚል በጋዜጣ ከታወጀ በኋላ የፈጠራ መብቴ ተከብሮልኛል፡፡
በአዕምሮዬ የሚጉላሉ በርካታ የፈጠራ ስራዎች አሉኝ ብለሀል፡፡ ወደፊት ልትሰራ ካሰብከው አንድ ሁለቱን ልትነግረኝ ትችላለህ?
ስራው በምስጢር የሚቆይ ነው፤ ነገር ግን ዝቅተኛ ኑሮ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ህይወት ቀላል የሚያደርግ ነው፡፡ ምን እንደሆነ ለመናገር አልፈልግም፤ ሰርቼ ስጨርስ… ልክ እንደ ሄሊኮፕተሯ እውን ሳደርግ… ያን ጊዜ አብረን ብናየው ይሻላል፡፡
የፈጠራ ሥራዎችህን በትምህርት ለመደገፍ አላሰብክም?
ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ አስተማሪ ፊትለፊቴ ቆሞ አያስተምረኝ እንጂ እኔ ሁሌም ራሴን እንዳስተማርኩት ነው፡፡ ለምሳሌ ስለኮምፒዩተር ኪ-ቦርድ አሰራር ማወቅ ብፈልግ ኢንተርኔት ውስጥ እገባለሁ፡፡ አስተማሪ ከሚያስረዳኝ አምስት እጥፍ በላይ ኢንተርኔት ያስተምረኛል፡፡ ከዚያ ቤቴ ሄጄ ያንን ለመስራት ሙከራ አደርጋለሁ፤ ስለዚህ እኔ ራሴን እያስተማርኩ ነኝ ብዬ ነው የማምነው፡፡
በመጨረሻ የምትለው ነገር ካለህ …  
የአንድን አገር መልካም ገፅታ ለመፍጠር ሁሉም በየዘርፉ ድርሻ አለው፡፡ አንቺ በጋዜጠኝነትሽ ስትበረቺ፣ እኔ በፈጠራዬ ስገፋ፣ መምህሩ በርትቶ ሲያስተምር፣ መሪዎች በአግባቡ ሀላፊነታቸውን ሲወጡ አገር መልካም ምስል ትይዛለች፡፡ ምሳሌ ልንገርሽ… ፎቶ ስታነሺ ወይም ስትነሺ አንቺ የምታይው ሙሉ ምስልሽን ነው፡፡ ነገር ግን ሜጋ ፒክሰሱ ትንንሽ ነጥቦችን ገጣጥሞ ነው ሙሉ ምስል ላንቺ የሚያሳይሽ። ይህ ማለት ኢትዮጵያ የሚለውን ሙሉ ምስል ለማምጣት የሁሉም ሰው ድርሻ (ትንንሽ ነጥቦች) መገጣጠም ስላለበት፣ መንግስት ለየትኛውም ሙያ ትኩረት ሰጥቶ ድጋፉን ቢቀጥል፣ ሙሉ የኢትዮጵያን ምስል ማየት እንችላለን፡፡ ሁሉም የድርሻውን ይወጣ። ሌላው በአገራችን ምርት ማመንና መኩራት አለብን። እኛ የሻይ ማሽን እየሰራን፣ ነጋዴዎች ከውጭ ያስገባሉ። ያገር ውስጥ ማሽን እንዳይገዛ እንቅፋት ይፈጥራሉ። መንግስት በእነዚህ ላይ ከፍተኛ ቀረጥ እየጣለ፣ በአገራቸው ምርት እንዲኮሩና የውጭ ምንዛሬ ያለአግባብ እንዳይባክን ማድረግ አለበት የሚል መልዕክት አለኝ። አመሰግናለሁ፡፡  

         የኮሪያው ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (ኮይካ)፣ ኤልጂ እና ዎርልድ ቱጌዘር የተባሉ ድርጅቶች፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር የፈጠራ ማዕከል ለማቋቋም በትጋት እየሰሩ መሆኑን አማካሪው ኮሚቴ አስታወቀ፡፡
የሕግ፣ የአስተዳደር፣ የሥልጠና ትብብር፣ የተማሪዎች አያያዝና የስትራቴጂክ ፕላን መመሪያዎች ተዘጋጅተው በግምገማ ሂደት ላይ መሆናቸውን የጠቀሰው ኮሚቴው፤ ጎን ለጎን የኮሌጅ ሕንፃ ግንባታም እየተካሄደና በመጪው መስከረም ወር መጨረሻ እንደሚጠናቀቅ ገልጿል፡፡
የኤልጂ ከፍተኛ የአመራር ቡድን፣ ከከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት፣ በስራው ከተሰማሩ ድርጅቶችና ከኢንዱስትሪው ባገኘው አስተያየትና ሐሳብ መሰረት፣ በየትም ቦታ እንደ ሞዴል ሊታይ የሚችል ኮሌጅ ማቋቋም ጠቀሜታው ከፍተኛ እንደሆነ መገንዘቡ ታውቋል፡፡
በሰንዳፋ ወረዳ የሚቋቋመው ኤልጂ ሆፕ መንደር፣ ዓላማው የተሻሻሉ ፕሮግራሞችን በመጠቀም፣ በሶስት ዓመት ውስጥ አካባቢውን ማሳደግ ለማህበረሰቡ አስፈላጊ የሆኑ የመሰረተ ልማት ሕንፃዎችን መገንባትና ራሱን በቋሚነት ማስተዳደር የሚችል የእርሻ መንደር መፍጠር ነው፡፡
እንዲሁም በዚሁ ስፍራ በኢትዮጵያ የሥራ እድል በመፍር ኢኮኖሚውን ለማሳደግ በኮይካ አማካይነት የሚቋቋመው የሙያ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት፣ የኤል ጂ ባለሙያዎች የተጠበቡበትን ቴክኖሎጂ በመጠቀም፣ ወደፊት በሙያ የተካኑ ኢንጂነሮችን ለመፍጠርና ለኮሪያ ዘማች ቤተሰቦች ነፃ የትምህርት ዕድል ለመስጠት እንደሚተጋ ታውቋል፡፡
በኤልጂና በኮይካ አማካይነት የሚሰራው የሦስት ዓመት ዕቅድ ኤልጂ የተካነባቸውን መሰረታዊ የኢንፎርሜሽ ቴክኖሎጂ ኮርሶች በማስተማር፣ በየዓመቱ 75 ባለሙያ ኢንጂነሮችን በኤሌክትሮኒክስና በሞባይል ስልክ ያስመርቃል ተብሏል፡፡
ወጣቶቹ በቤትና በቢሮ፣ የኤሌክትሮኒክ ኮሙኒኬሽንና መልቲ ሚዲያ ቁሳቁሶችና ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ የሚሰለጥኑ ሲሆን፣ በሦስቱም የሙያ መስክ 25፣ በአጠቃላይ 75 ወጣቶች ይመረቃሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለተማሪዎቹ ነፃ ምሳ የሚቀርብ ሲሆን፣ እንደ ፈጠራ፣ ጤና፣ የስራ አመራር፣… ያሉ መሰረታዊ የዝንባሌ ሥልጠናዎች በየሳምንቱ ለአንድ ሰዓት ይሰጣቸዋል።
ሰልጣኞቹ 10ኛ ክፍልን ያጠናቀቁና የ10 ክፍል ተማሪ መሆን ያለባቸው ሲሆን እያንዳንዱ ሰልጣኝ 100 ብር መክፈል አለበት፡፡ ከሰልጣኞቹ መካከል 10 በመቶ ያህሉ የኮርያ ዘማቾች ቤተሰብና የመክፈል አቅም የሌላቸው የድሃ ልጆች ሲሆኑ ክፍያው አይመለከታቸውም፡፡  


====================

ወቅታዊ የቢዝነስና ኢኮኖሚ መፃህፍት

The Divide - በማት ታይቢ
Lean in  - በሼሪል ሳንድበርግ
Thrive  - በአሪያና ሃፊንግተን
The Confidence code - በካቲ ካይና ክሌይር ሺፕማን
Think like a Freak - በስቲቨን ዲ.ሌቪትና ስቲፈን ጂዱብነር
David and Goliath - በማልኮልም ግላድዌል
Creativity, Inc.  - በኢዲ ካትሙል
Capitalist in the Twenty First Century    -  በቶማስ ፒኬቲ
Stress Test - በቲሞቲ ጌይትነር
The Wolf of wall Street - በጆርዳን ቤልፎርት
Flash Boys - በማይክል ልዊስ
(Forbes መፅሄት ሰሞኑን ባወጣው ዕትሙ እነዚህን የመፃህፍት ዝርዝር የንባብ አማራጮች አድርጎ አቅርቧቸዋል)

ወላጆች ለልጆች እግር መበላሸት ተጠያቂ ናቸው ተባለ
         በቅርቡ የተካሄደ ጥናት፤ በዓለም ላይ 4ሚ. ያህል ህፃናት ልካቸው ያልሆነ በመጫማት እንደሚሰቃዩ ይጠቁማል፡፡ ለዚህ ደግሞ ተጠያቂዎቹ ወላጆች ናቸው ይላል፡፡
የልጆቻቸውን እግሮች ልካቸው ያልሆነ ጠባብ ጫማ ውስጥ እንዲሰቃዩ የሚፈቅዱ ወላጆች፤ ለልጆቻቸው የዘላለም ችግር እያስቀመጡላቸው እንደሆነ ማወቅ አለባቸው ብሏል ጥናቱ፡፡ ጠባሳ፣ እብጠት፣ የጣት ጥፍር ወደ ውስጥ ማደግ… የአጭር ጊዜ ችግሮች ሲሆኑ የረዥም ጊዜ ችግሮች ደግሞ የእግር መንጋደድ ለምሳሌ የጣት መቆልመም እንዲሁም የጉልበትና የቅርጽ መበላሸት እያለ ዝርዝሩ ይቀጥላል፡፡
ወላጆች ለልጆቻቸው ጥርስ ብዙ እንክብካቤ የሚያደርጉትን ያህል ለእግሮቻቸውም ሊያስቡላቸውና ሊጠነቀቁላቸው ይገባል ይላሉ፤ የእግር ጤናና እንክብካቤ ባለሙያዎች፡፡ ለመሆኑ 4ሚ. ህፃናት ለምንድነው ልካቸው ባልሆነ ጫማ የሚሰቃዩት? በቸልተኝነት? በገንዘብ እጥረት? በአመቺነትና ፋሽን በመሆኑ? ሁሉም ሰበብ ይሆናሉ ይላሉ ብለዋል በግላስጐው ካሌዶንያን ዩኒቨርሲቲ፣ በእግር ጤናና እንክብካቤ ዙሪያ ሌክቸር የሰጡት ዶ/ር ጐርዶን ዋት፡፡
የህፃናት እግሮች በዕድሜያቸው የመጀመያዎቹ አራት ዓመታት በፍጥነት የሚያድጉ ቢሆንም  የእግራቸው አጥንቶች፣ ጡንቻዎችና መገጣጠምያዎች እንደ አዋቂ እግር ለመጠንከር ግን እስከ 18 ዓመት ድረስ ሊወስድባቸው ይችላል የሚሉት ባለሙያዎቹ፤ የታዳጊዎችም ሆነ የህፃናት እግሮች በቂ ትኩረትና እንክብካቤ እንደሚሹ ያሳስባሉ፡፡  በጥናቱ እንደተጠቆመው፤ ከ10 ወላጆች አንዱ ልጆቹ ለእግራቸው የሚያንሳቸውን ጫማ አሁንም ድረስ እንደሚያደርጉ ሲናገር፣ ገሚሶቹ ወላጆች ደግሞ፤ ልጆቻቸው “ጫማው እግራችንን አሳመመን” ብለው እስኪጨቀጭቋቸው ድረስ አዲስ ጫማ እንደማይገዙላቸው ታውቋል፡፡
የእግር ህክምና ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ ብዙ ሰዎች ለልጆቻቸው እግር ጥንቃቄ የማያደርጉት ጠባብ ጫማ መጫማት የሚያስከትለውን ችግር ስለማይረዱት ነው፡፡ ለዚህ ጥናት ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው ወላጆች ውስጥ 40 በመቶ ብቻ ናቸው የልጆቻቸው ጫማ ልካቸው እንደሆነና ምቾት እንዳለው ለማረጋገጥ የሚተጉት ተብሏል፡፡
ልጆች ጫማ በተገዛላቸው ቁጥር እግራቸው መለካት እንዳለበት የሚያሳስቡት ባለሙያዎቹ፤ ወላጆች ጫማው ላይ የሰፈረውን ቁጥር ብቻ አይተው መግዛት እንደሌለባቸው ይመክራሉ፡፡

Published in ዋናው ጤና

ጤናንና ህይወትን ለመታደግ ነው ተብሏል
ሲጋራ ማጨስ ለከፍተኛ የጤና አደጋ፣ ባስ ሲልም ለህልፈት እንደሚዳርግ ማንም ሊክድ አይችልም። እንዲያም ሆኖ ከወደ አየርላንድ የተሰማው አዲስ እገዳ ክፉኛ ያስደነገጠው ከአጫሾች ይልቅ የትምባሆ ኩባንያዎችን ነው። ሰሞኑን አየርላንድ ማንኛውም ሲጋራ ስያሜ፣ የንግድ ምልክትና አርማ እንዳይኖረው የሚያግድ ህግ  አውጥታለች፡፡ እገዳው ሲጋራዎች ላይ ብቻ ግን አይደለም፤ የሲጋራ ፓኮዎችም ያለምንም ፅሁፍና ምልክት ለገበያ እንዲቀርቡ ህጉ ያስገድዳል። አዲሱ ህግ የትምባሆ ኩባንያዎችን ቢያስከፋም የአየርላንድ የጤና ሚኒስትር ጄምስ ሬይሊ፤ እገዳው የብዙዎችን ህይወት ለመታደግ ያግዛል ብለዋል፡፡
የምርት ስያሜ፣ የንግድ ምልክትና አርማ ያለው ሲጋራ ለሸማቶች እንዳይቀርብ የሚያግድ ህግ በማጽደቅ አየርላንድ በአውሮፓ የመጀመሪያዋ አገር ናት ተብሏል፡፡
አውስትራሊያ ተመሳሳይ እገዳ በሲጋራ ላይ በመጣል ከዓለም የመጀመሪያዋ አገር ስትሆን ኒውዚላንዶች ደግሞ በረቂቅ ህጉ ላይ እየተከራከሩ እንደሆነ ታውቋል፡፡ እንግሊዝን ጨምሮ ሌሎች የአውሮፓ አገራት እገዳው በህግ የመውጣቱን አስፈላጊነት ገና እያጤኑት ነው ተብሏል፡፡
የአየርላንድ ጤና ሚኒስትር በሰጡት መግለጫ፤ “የህጉ ዓላማ የሲጋራ ፓኮዎች ለሸማቾች ያላቸውን ማራኪነት በመቀነስ፣ በጤና ላይ የሚያደርሱትን አደጋ ማጉላት ነው፡፡ ፓኬቶች ሰዎችን በተለይ ህፃናትን የማሳሳት አቅማቸውን በመቀነስ የማጨስ ጐጂነትን እንዲገነዘቡ እናደርጋለን” ብለዋል፡፡
የትምባሆ ኩባንያዎች ግን እገዳውን አጥብቀው ተቃውመዋል፡፡ የትምባሆ ምርቶችን ስያሜና አርማ አልባ አድርጐ ማቅረብ፣ ሃሰተኛ የሲጃራ ምርቶችን የሚያመርቱ ወንጀለኞችን የሚያግዝና የሚያበረታታ ነው ብለዋል - ኩባንያዎቹ፡፡
ቤንሰን ኤንድ ሄጅስ እና ደንሂል በሚሉ ስያሜዎች የሚታወቁት ሲጋራዎች ባለቤት የሆነው የብሪቲሽ አሜሪካን ቶባኮ (BAT) ቃል አቀባይ እንደተናገሩት፤ የአየርላንድ ካቢኔ ረቂቅ ህጉን ማጽደቁ አሳዝኗቸዋል።
“ምንም ፅሁፍ ያልሰፈረበት ሌጣ ፓኬት፣ ታዳጊዎች ሲጋራ እንዳይጀምሩ ወይም አጫሾች ማጨስ እንዲያቆሙ ስለማድረጉ ተዓማኒ ማስረጃ የለም” ሲል ተሟግቷል  ተቋሙ፡፡
በቅርብ ዓመታት ሲጋራ ማጨስ በህብረተሰቡ ላይ የጋረጠውን አደጋ ለመቅረፍ የሚያስችል ውይይት ያደረገችው አየርላንድ፤ እ.ኤ.አ በ2004 ዓ.ም በስራ አካባቢ ሲጋራ ማጨስን ሙሉ በሙሉ የሚያግድ ህግ በማውጣት በዓለም የመጀመርያው አገር ሆናለች፡፡ በሥራ አካባቢ ሲጋራ ማጨስ የሚከለክለው ህግ መሸታ ቤቶችንና ክለቦችንም እንዳካተተ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ እንዲያም ሆኖ ታዲያ የህጉ ተፈፃሚነት 97 በመቶ እንደተሳካ ተገልጿል፡፡

Published in ዋናው ጤና
Saturday, 14 June 2014 12:06

የቸኮሌት ነገር!

የደም ግፊትን ይቀንሳል
በኮኮዋ ውስጥ የሚገኙት ፍላቫኖልስ የተባሉት ንጥረ ነገሮች የደም ግፊት የሚቀንሱ መድሃኒቶችን ሥራ እንደሚሰሩ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ ፍላቫኖልስ ሰውነታችን ናይትረስ ኦክሳይድ እንዲያመርት በማድረግ ለደም ስሮች መከፈት እገዛ ያደርጋሉ፡፡
የአውስትራሊያ ተመራማሪዎች፤ ኮኮዋ ዘወትር መጠቀም የሰዎችን የደም ግፊት ዝቅ እንደሚያደርግ በጥናታቸው ያረጋገጡ ሲሆን 1 በመቶ ያህሉ ግን ቸኮሌትን ከመጠን በላይ በመመገብ ለሆድ ህመም መጋለጣቸውን በጥናት ወረቀታቸው ላይ አስፍረዋል።
የጉበት ጉዳትን ይከላከላል
ቸኮሌት ለደም ግፊት ያለው ጠቀሜታ የሚመነጨው በውስጡ ካለው ከፍተኛ የፍላቫኖል ይዘት  ነው፡፡ በጉበት ቬይኖች ከፍተኛ የደም ግፊት መከሰት ከጉበት ጉዳት ወይም ሥር ከሰደደ የጉበት በሽታ ጋር እንደሚገናኝ ይታመናል፡፡ ቀደም ሲል የተደረገ ጥናት እንደሚጠቁመው፤ ጥቁር ቸኮሌት መብላት በጉበት ውስጥ ያለውን የደም ዝውውር ያሻሽለዋል፡፡ ይኼው የቸኮሌት ዓይነት የጉበት ጉዳትን መከላከል ይችል እንደሆነ ለማረጋገጥ በአሁኑ ወቅት ጥናቶች እየተካሄዱ እንደሆነ ታውቋል፡፡
ለልብ ጤንነት ይጠቅማል
የደም ግፊትን ዝቅ በማድረግ፣ የደም ስሮችን በመክፈትና፣ ብግነትን በመቀነስ ከፍተኛ ሚና የሚጫወተው ቸኮሌት፤ የልባችንን ጤንነት በመጠበቅ ረገድም ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል። የልብ በሽታንና ስትሮክንም ይከላከላል፡፡ ከ114ሺ በላይ በሆኑ ሰዎች ላይ በተካሄደው ጥናት፤ ብዙ ቸኮሌት የሚመገቡ ሰዎች እጅግ አነስተኛ ከሚመገቡት ይልቅ በልብ በሽታ የመያዝ ዕድላቸው 37 በመቶ፣ ለስትሮክ የመጋለጥ ዕድላቸው ደግሞ 29 በመቶ እንደቀነሰ ተረጋግጧል፡፡
ሸንቃጣ ያደርጋል
ከ1ሺ በሚበልጡ  ሰዎች ላይ በተደረገ ጥናት እንደተረጋገጠው፤ ቸኮሌት መብላት የሚያዘወትሩ ሰዎች ሸንቃጣ የመሆን ዕድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡
ለጥናቱ የተመረጡት ሰዎች “በሳምንት ስንት ጊዜ ቸኮሌት ትመገባለህ/ትመገቢያለሽ?” የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ሲሆን የጥናት ውጤታቸውን በ “አርካይቭስ ኦፍ ኢንተርናል ሜዲሲን” ያሳተሙት ተመራማሪዎች፤ በሳምንት ውስጥ ደጋግመው ቸኮሌት የሚበሉ ሰዎች አልፎ አልፎ ከሚበሉት የበለጠ ሸንቃጣ እንደሆኑ አረጋግጠዋል ፡፡
ብልህና ብሩህ ያደርጋል
በ”ኒው ኢንግላንድ ጆርናል ኦፍ ሜዲሲን” የወጣ አንድ ጥናት፤ ቸኮሌት በብዛት የሚጠቀሙ ህዝቦች ያላት አገር፣ ከሌሎች የበለጠ የኖቤል ሽልማት አሸናፊዎች እንደሚኖራት አመልክቷል፡፡ ቸኮሌት አዘውትሮ መብላት ብልህና ብሩህ ያደርጋል ማለት ነው፡፡ ለዚህም በምሳሌነት የተጠቀሰችው ስዊዘርላንድ ናት፡፡
ስዊዘርላንዶች ቸኮሌት በብዛት በመመገብ የሚታወቁ ሲሆን ብዙ የኖቤል ተሸላሚዎች እንዳሏቸውም ተገልጿል፡፡ የእንግሊዝ ተመራማሪዎች እንደሚሉት፤ በእንግሊዝ የኖቤል ተሸላሚዎችን ለማብዛት እያንዳንዱ ሰው በዓመት 2 ኪ.ግ ቸኮሌት መብላት ይኖርበታል፡፡

Published in ዋናው ጤና

          “ከመጣሁ ስድስት ቀን ሆኖኛል፤ ኮንሶን በጣም ወድጃታለሁ፤ ኒውዮርክ የተባለውን ቦታ ጐብኝቼ ማመን አቅቶኛል፣ ባህላዊ መንደሮች ለማመን የሚያዳግቱ ናቸው። የህዝቡ ትህትናና ለስራ ያለው ፍቅር ልዩ ነው፡፡ ብዙ ለመቆየት አስቤ ነበር፤ ነገር ግን ፍላጐቶቼ አልተሟሉም። ቢሆንም ወደፊት ችግሮቹ ተስተካክለው አመቺ ሲሆኑ ከጓደኞቼ ጋር ተመልሼ ለመምጣት አስቤያለሁ” (የ29 ዓመቷ የቡልጋሪያ ዜጋ ማሪያና አዶልፍ)፡
ኮንሶ ከአዲስ አበባ በ595 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ወረዳ ስትሆን ካራት የተባለች የወረዳዋ መዲና ላይ ቱሪስቶች መዳረሻቸውን ያደርጋሉ። በወረዳው ዘጠኝ ያህል ጐሳዎች የሚገኙ ሲሆን “አፋኾንሶ” የተባለ ከኦሮምኛ ጋር የቅርብ ዝምድና ያለው ቋንቋ ይናገራሉ። እጅግ ማራኪ ትህትና ያለው የኮንሶ ማህበረሰብ፤ በስራ ታታሪነቱ የሚታወቅ ሲሆን በሸለቆና በተራራ የተከበበውን አስቸጋሪ መልክአ ምድር በአገር በቀል እውቀቱ በእርከን ስራ አፈሩን ከመሸርሸር አድኖ፣ ተራራማውን መሬትም አስውቦ በስፋት በእርሻ ስራ የሚተዳደር ማህበረሰብ ነው፡፡ የኮንሶ ህዝብ የራሱ ባህል፣ የዳኝነት ስርዓት፣ አለባበስ እና ጭፈራ ያለው ሲሆን በተለይም የተፈጥሮ መልክአ ምድሩ በ2003 ዓ.ም በዩኔስኮ ከተመዘገበ በኋላ ቱሪስቶችን የመሳብ ጅምር እየታየና ከዘርፉም በዓመት እስከ አንድ ሚሊዮን ብር እንደሚሰበሰብ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ይሁን እንጂ የኢንተርኔት፣ የመብራትና የውሃ ችግር የኮንሶ ህዝብ ተግዳሮቶች ናቸው፡፡ ከቡልጋሪያ የመጣችው ቱሪስት ማሪያና አዶልፍ፤ ፍላጐቶቼ አልተሟሉም ያለችው ያለ ምክንያት አይደለም። የኮንሶ መዲና ካራት ገና በማደግ ላይ ያለች ከትንንሽ ከተሞች የምትመደበ ከተማ ናት፡፡ በአሁኑ ሰዓት በከተማዋ ስድስት ሆቴሎችና ሁለት ሎጆች ብቻ ናቸው ያሉት፡፡ ያም ሆኖ በአስደናቂ ተፈጥሮ የተከበበችው የኮንሶ ወረዳ፤ በአለም ቅርስነት የተመዘገቡ ልዩ ተፈጥሮዎች አሏት፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ከ300 ዓመት በፊት በንፋስ ተሸርሽሮ የተለያዩ የህንፃ ቅርፆችን ይዞ የቀረውና “ኒውዮርክ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ቦታ አንዱ ሲሆን ከካራት ከተማ በ17 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ አፈር እንዳይሸረሸር በዘየዱት መላ ተፈጥሮን ምቹ ያደረጉበት የእርከን ስራቸው ሲሆን ሶስተኛው ባህላዊ ከተሞቻቸው (አምባ መንደሮቻቸው) በዓለም ቅርሰነት ተመዝግበዋል። ለዚህም ነው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የባህል፣ የትምህርትና የሳይንስ ተቋም (ዩኔስኮ) በካራት ከተማ እምብርት ላይ “ኮንሶ የአለም ቅርስ መገኛ” የሚል ሀውልት ያቆመው፡፡ የኮንሶ ወረዳም ይህንኑ በማስመልከት ቅርሶቹ የተመዘገቡበት ሰኔ ወር መዳረሻ ላይ በየአመቱ የባህል ፌስቲቫል ያዘጋጃል፡፡ ዘንድሮም ከግንቦት 23 እስከ 26 ቀን 2006 ዓ.ም የቆዬ የባህል ፌስቲቫል በካራት ከተማ የተካሄደ ሲሆን፤ ዘጠኙም ጐሳዎች የተገኙበት የጐዳና ላይ ትዕይንት፣ የካራት ዲስትሪክት ሆስፒታል ምረቃ፣ የስድስት ጤና ጣቢያዎች ምረቃ፣ የከተማ አስተዳደሩ እና ዘመናዊ ቤተ መጽሐፍት ለመገንባት ሁለት የመሰረት ድንጋዮች የማስቀመጥ ስነ-ስርዓት ተከናውኗል፡፡ ለኮንሶ ህፃናት ግንዛቤ የሚውል “ኮንሶን ለህፃናት” የተሰኘ የቱሪዝም መጽሐፍና “ሴራኦታ ኮንሶ” የተባለ የኮንሶ ብሔረሰብ የባህል ህግ ስርዓትን የሚያስቃኝ መጽሐፍ ምረቃም የዘንድሮው ፌስቲቫል አካላት ነበሩ፡፡
በበዓሉ ለመታደም ወደ ኮንሶ ከተጓዙት ጋዜጠኞች አንዷ ነኝ፡፡ ኮንሶ ስሄድ የመጀመሪያዬ ነው። የህዝቡ አቀባበል፣ ትህትናው በጣም ይማርካል፡፡ ካራት ከተማ እንግዶቿን ለመቀበል አደባባዩ ላይ ዳስ ጥላ ትጠብቃለች። ሁሉም ደስ ይላል፡፡ እኔ ከተማዋን ወድጃታለሁ ደግሞ የሚጐድላት አለ፤ ለዚህች ከተማ ልቀኝላትም ዳዳኝ፡፡ ኔትዎርክ የለም እንጂ ኔትዎርክ ቢኖር ከትሞ መቀመጥ ኮንሶ ላይ ነበር… አልኩኝ ለራሴ፡፡
ኒዮርክን ለመጐብኘት በሄድንበት ጊዜ አይን አፍዝዝ፣ ተፈጥሮው በግርምት አፍን እጅ ላይ ያስከድናል። በድፍረት ገደሉን ወርደን እስከ ዋናው ኒውዮርክን መሳይ የአፈር ህንፃ የሰራው ዋሻ ድረስ ሄድኩኝ፡፡
እጄን ይዞ ገደሉን ያወረደኝ የግብርና ባለሙያ የሆነው የኮንሶ ወጣት፤ “ሚኪያ በሀይሉ ‹ደለለኝ› የሚለውን ዘፈን እዚህ ቦታ ላይ ነበር የዘፈነችው፤ ስትሞት እዚህ ቦታ ላይ ተሰብስበን አለቀስን” በማለት የዘፈኑ ክሊፕ የተሰራበትን ቦታ በእጅ ጠቆመኝ፡፡ ጐብኝተን ስንጨርስ ያንን ያገጠጠ ገደል ወጥተን ጫፍ ላይ ስንደርስ፣ ድካሙ ውሃ ውሃ ቢያሰኘንም ጫፉ ላይ የሚላስ የሚቀመስ አልነበረም። ለምን ብለን ስንጠይቅ ከአስጐብኚዎቻችን አንዱ “እዚህ በታ ላይ የምታያቸውን ሁለት ጐጆዎች፣ ከተማ አስተዳደሩ የሰራቸው ለጐብኚዎች ማረፊያ እንዲሆኑና ሻይ ቡና፣ ለስላሳና ውሃዎች እንዲሸጡበት ታስቦ ቢሆንም ለምን እንደተረሱ አላውቅም አለኝ”። በቃ ቱሪዝም አልገባንም ማለት ነው? ብዬ ራሴን ጠየቅሁኝ፡፡ ከኒዮርክ ስንመለስ ዩኔስኮ በለም ቅርስነት የመዘገባቸውን ባህላዊ ከተሞች በኮንሶዎች አጠራር (ፓሌታዎችን) ጐበኘን፡፡ አይን አፍዝዙ ባህላዊ መንደር እንዴት ተመሠረተ? የካቡ አጥር እንዴት ረዘመ? የካቡ ክብነት ከምን የመጣ ነው? የሚለውና መሰል በአምባ መንደሮቹ ውስጥ የሚገኙ ልዩ ልዩ ትሩፋቶች በግርምት አቅልን ያስታሉ፡፡ እስቲ ከመንደሮቹ አንዱ የሆነውን የጋሞሌን ባህላዊ መንደር ላስቃኛችሁ፡፡
የጋሞሌ ባህላዊ ከተማ (ፓሌታ)
አቶ ገረሱ ካውሶ ቀደም ሲል የኮንሶ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሀላፊ የነበሩ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሶሻል አንትሮፖሎጂ የሁለተኛ አመት ተማሪ ናቸው፡፡ እንደ አቶ ገረሱ ገለፃ፤ አምባ መንደሮቹ እረጅም እድሜ ያላቸው ሲሆኑ ከ800 ዓመት በላይ ያስቆጠሩ ናቸው፡፡ አምባ መንደሮቹ ከ35 በላይ ቢሆኑም ዩኔስኮ በናሙናነት በአለም ቅርስነት የመዘገባቸው 12ቱን ነው። ከእነዚህም መንደሮች አንዱ “ጋሞሌ” የተባለው ባህላዊ ከተማ (ፓሌታ) ሲሆን ይህ መንደር ዘጠኝ ዙር ክብ የካብ አጥሮች አሉት፡፡ የካብ አጥሮቹም በጣም ከፍታ ያላቸው ሲሆኑ ከሌላው ከተማ ጐላ ብሎም ይታያል። “ቀደምት የፓሌታዎቹ መስራች አያቶች ከብዙ ነገር ጋር ትግል ነበረባቸው፡፡ እርስ በእርሳቸው ይጋጩ ነበር፡፡ ከዱር አውሬዎችም ጋር ይታገሉ ነበር፡፡ አነዚህን ነገሮች ለመከላከል ተሰብስበው መንደር ለመመስረትና ትልልቅ የድንጋይ ካብ አጥሮችን ለመካብ ተገደዋል” ይላሉ አቶ ገረሱ ካውሶ፡፡ እንደ ባለሙያው ገለፃ፤ ክብ ክብ የካብ አጥሮቹ ዘጠኝ ዙር ሲሆኑ ዘጠኝ ትውልድን ይወክላሉ፡፡
የመጀመሪያዎቹ መስራቾች መሃል ላይ ቤታቸውን ሰርተው ዙሪያውን በትልቅ የድንጋይ ካብ ሲያጥሩ፣ ከእነሱ የሚወለዱት ራሳቸውን ችለው ከዚያ ክብ ይወጡና የራሳቸውን ሌላ ክብ መንደር ይፈጥራሉ፡፡ የልጅ ልጆችም እንዲሁ፡፡
የጋሞሌ መንደርም ዘጠኝ ክብ አጥሮች ያሉት ሲሆን ዘጠኝ የልጅ ልጅ ልጅ ሀረጐች እንዳሉት ያሳያል፡፡ በፓሌታዎቹ ውስጥ ሞራዎች፣ ኦላሂታ፣ ካዎ እና መሰል ባህላዊ ነገሮች ይገኛሉ፡፡ በእነዚህ መንደሮች ጉብኝት ሲያደርጉ ድንገት ሳት ብሎዎት አንዱ መንገድ ውስጥ ከገቡ ተመልሰው ለመውጣት ማጣፊያው ያጥረዎታል። አብረው ለጉብኝት ከሄዱት ጓደኞችዎ ጋር ተመልሰው ለመገናኘት የሰዓታት ፍለጋ ሊያስፈልግ ይችላል፡፡
የፓሌታዎቹ ሞራዎች
የኮንሶ ማህበረሰብ ጥብቅ የሆነ የአስተዳደር ስርዓት ያለው ሲሆን ከላይ እስከታችም የራሱ መስመር ያለው ሲሆን ይህን ልምድና ወጉን የሚካፈልበት፣ ራሱን የቻለ ማዕከል ያለው ነው፡፡ ይህ ማዕከል ዘርፈ ብዙ አገልግሎት እንዳለው የስነ - ማህበረሰብ ባለሙያው አቶ ገረሱ ይናገራሉ፡፡ አደባባዩ “ሞራ” ተብሎ የሚጠራ ሲሆን የማህበረሰብ መሰብሰቢያ አደባባይ ነው፡፡ በዚህ ሞራ ላይ አዋጅ ይነገራል፣ እርቅ ይከናወናል፣ ውይይቶችና የተለያዩ ስምምነቶች ይደረጋሉ፡፡ ከጐሳ መሪዎች የሚወጡ መልዕክቶች ለህብረተሰቡም ይተላለፉበታል። ሞራ ከዚህም ባለፈ ህፃናትና ወጣቶች ከትልልቅ አባቶች የህይወት ልምድ የሚካፈሉበት ቦታ ሲሆን የህይወት ክህሎትም የሚማሩበት እንደሆነ ባለሙያው ይናገራሉ፡፡ “በሞራዎቹ ዙሪያ አባቶች ተሰብስበው ለመንደሩ ህፃናት ተረት ያወራሉ፣ እኔ ሞራ ላይ ተረት ተምሬያለሁ፣ አባቶች ክራር ይዘው የህፃናት ጭፈራ ይለማመዳሉ” ያሉት ባለሙያው፤ ህፃናት ሲጨፍሩ ጭፈራውን የሚገመግም አካል፣ ሞራ ላይ ተቀምጦ “ይሄ ትክክል ነው፤ አይደለም” በሚል አስተያየት እንደሚሰጥና የባህላዊ አይዶል ሾው አይነት ባህሪ እንዳለው በጉብኝቴ ወቅት አቶ ገረሱ አጫውተውኛል፡፡ በሞራው (በአደባባዩ) መሀል ላይ የመኝታ ቆጥ ያለው ትልቅ ሳር ቤት የሚገኝ ሲሆን በመኝታው ላይ የመንደሩ ወጣቶችና አልፎ አልፎ አባቶችም ተቀላቅለው ያድሩበታል፡፡
የማደሪያ ሳር ቤቱ ጥቅም ዘርፈ ብዙ ነው፤ እንደ ባለሙያው ገለፃ፡፡ አንደኛ ወጣቶቹ ተሰብስበው ሲያድሩ በመንደሩ የእሳት አደጋ ቢነሳ፣ አውሬ መንደር ውስጥ ገብቶ ጉዳት ሊያደርስ ቢሞክር፣ ባልና ሚስት ተጣልተው ጩኸት ቢነሳ፣ ከተሰበሱበበት ወጥተው ለተከሰተው ችግር አፋጣኝ መፍትሔ ለመስጠት ያመቻቸዋል። ሁለተኛው ምክንያት የኮንሶ ህዝብ የመከላከያ የካብ አጥሮቹን የሚሰራው ትልልቅ ድንጋዮችን በሸክም ከሩቅ ቦታ እያመጠ በመሆኑ፣ በየቀኑ ከሚስቱ ጋር እያደረ የግብረ ስጋ ግንኙነት በማድረግ፣ ጉልበቱን እንዳያደክም ይረዳዋል፡፡ ሶስተኛውና አስገራሚው ምክንያት ደግሞ ቀደም ሲል የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ባልነበረበት ጊዜ ሚስት ቶሎ ቶሎ እየወለደች የቤተሰቡ ቁጥር በዝቶ ችግር ላይ እንዳይወድቁ፣ እንደ ቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ይጠቀሙበት ነበር - የወጣቶቹን በሞራው ሳር ቤት ውስጥ ማደር፡፡ በሌላ በኩል ሌሊት ወጣቶቹ ከአባቶች ጋር ሲያድሩ በርካታ ጉዳዮችን እያነሱ እንዲወያዩ ይረዳቸዋል፡፡
የሞራ አይነቶች
የኮንሶ ማህበረሰብ አደባባዮች (ሞራዎች) ሶስት አይነት ናቸው፡፡ አንደኛው ቀለል ያለ ሆኖ በየንኡስ መንደሮቹ የሚገኝ ሲሆን ሰዎች በየቀኑ ተሰብስበው ይጨዋወታሉ፤ ጨቃ የተባለውን ባህላዊ መጠጥ ይጠጣሉ፡፡ ከስራ በኋላ አየር ለመቀበል በሞራው ዙሪያ ተሰባስበው ገበጣ የተባለውን ባህላዊ ጨዋታ ይጫወታሉ። በጉብኝቴም ወቅት ይህንኑ አስተውያለሁ። ሁለተኛው የሞራ አይነት የእምነት አገልግሎት የሚሰጥበት ሲሆን የተጣሉ ሰዎች የሚማማሉበት ነው፡፡
በአካባቢው ከብት ሲጠፋ፣ ሰው ሞቶ ሲገኝና ሌላ ንብረት ሲጠፋ፣ የገደለው ወይም የሰረቀው ሰው ተሰውሮ ካደረገው የተጠረጠረው ሰው ወደ ሞራው ይቀርባል፡፡ በሞራው ውስጥ የመሀላ ድንጋዮች የሚገኙ ሲሆን የተጠረጠረው ሰው “ይህን በደል ፈጽሜ ከሆነ እግዚአብሔር ይፍረድብኝ” ሲል መሀላ ይፈጽማል። በማህበረሰቡ አንድ ሰው በውሸት ሞራ ላይ ቀርቦ ድንጋዮቹን ነክቶ ከማለ በደቂቃዎች ውስጥ ይቀሰፋል ተብሎ ስለሚታመን ማንም ሰው በውሸት እንደማይምል አቶ ገረሱ ይናገራሉ፡፡ ይህ ሞራ በተጨማሪም በአዝመራ ወቅት ዝናብ ሲጠፋና የተዘራ ሰብል ሲደርቅ፣ የአገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶች ተሰብስበው ፈጣሪያቸውን ዝናብ እንዲያዘንብና ከድርቅ እንዲያድናቸው የሚለማመኑበት የፀሎት ስፍራም ነው፡፡
ሶስተኛው አይነት ሞራ ትልልቅ አመታዊ በዓላት ሲከበሩ ብቻ የሚያገለግል ሲሆን ከበዓላቱ አንዱ የትውልድ የስልጣን ርክክብ በዓል ነው። በ18 ዓመት አንዴ የሚከናወነውና በማህበረሰቡ “ኸልዳ” ተብሎ የሚጠራው በዓል 18 አመት ማህበረሰቡን ሲያገለግል ከቆየ በኋላ ስልጣኑን ለሌላ አዲስ ትውልድ በሚያስረክብበት ጊዜ በዚህ ሞራ ውስጥ ይካሄዳል። 18 አመት ስልጣን ይዞ ህዝቡን ሲመራ የነበረው ትውልድ፤ ለአዲሱ ሲያስረክብ “እኛ ይህንን ሰርተናል እናንተ የተሻለ ስሩ፣ ተባረኩ” ብሎ በሰላማዊ መንገድ ስልጣኑን ያስረክባል። መራቂ ሽማግሌም በትልቅ ጐድጓዳ እቃ ወተት ከያዘ በኋላ፣ በአበባ ወተቱን ነክሮ እየረጨ ቡራኬ ይሰጣል፡፡ አደራም ይጥላል፡፡ ይህ የስልጣን ርክክብ የሚካሄድበትና ሌላ በዓላት ሲኖሩ ብቻ የሚከፈት አደባባይ (ሞራ) ነው፡፡
“ኦላሂታ”
በኮንሶ ህዝቦች “ኦላሂታ” የሚል መጠሪያ ያለው ሲሆን የትውልድ የስልጣን ፖል ነው፡፡ 18 ዓመት ካገለገለው ትውልድ አዲስ ስልጣን የሚረከበው ትውልድ ስልጣን ሲረከብ የራሱን የትውልድ ፖል (ኦላሂታ) ሞራው በሚገኝበት አደባባይ ይተከላል፡፡ ይህ የትውልዱ ማስታወሻ ነው፡፡
ለኦላሂታ የሚያገለግለው እንጨት ፅድ ሲሆን ከየትኛውም ቦታ በዘፈቀደ የሚቆረጥ እንዳልሆነ አቶ ገረሱ ይናገራሉ፡፡ ዛፉ በጐሳ መሪዎች መኖሪያ አካባቢ በጥብቅ ደንነት የሚጠበቅ ሲሆን ምስጥ የማይበላውና የማይበሰብስ መሆኑ ተረጋግጦና በጐሳ መሪዎች ተባርኮ እንደሚቆረጥም ይነገራል። ስልጣኑን ሲረከብ ይህን ፖል (ኦላሂታ) የተከለው ትውልድ 18 አመት ካገለገለ በኋላ ስልጣኑን ሲያስረክብ  መጪው አዲስ ትውልድ ስልጣን ሲይዝ የመጀመሪያው አስረካቢ ፖል የተከለበት ጐን አዲስ ኦላሂታ ተክሎ ስልጣኑን ይረከባል፡፡ በጉብኝቴ ወቅት የተለያዩ ትውልዶች ስልጣን ሲይዙ የተከሏቸው ፖሎች እጅብ ብለው ቆመው ባንዲራ ተሰቅሎባቸው ተመልክቻለሁ፡፡
“ዋካዎች”
በኮንሶ ማህበረሰብ ዋካዎች የሚባሉት በአካባቢው ጀብድ ለሠራ፣ በጦርነት ድል ለነሳ፣ አንበሳና ነብር ለገደለ በአጠቃላይ በማህበረሰቡ ውስጥ ትልቅ ሚና ተጫውቶ ላለፈ ሰው የሚተከሉ ሶስት ትክል ረጃጅም ድንጋዮች ሲሆኑ እነዚህ ድንጋዮች ለጀብደኛው እንደ ሀውልት ሆነው በሞራው ፊት ለፊት ከኦላሂታዎቹ (ፖሎቹ) ጐን ይገኛሉ። በነገራችን ላይ ካራት ከተማ ውስጥ ከዋናው አደባባይ አለፍ ብሎ አውላላ ሜዳ ላይ የተተከሉ ሶስት ድንጋዮች አይቻለሁ፡፡
በእለቱ በከተማዋ የሚውለውን የሰኞ ገበያ ለመጐብኘት ስንሄድ ነው ዋካዎቹን የተመለከትኳቸው። አንዱን የአካባቢውን ተወላጅ፣ ስለ ዋካዎቹና ለማን እንደተተከሉ ስጠይቀው፤ “ለጓድ መለሴ የተተከሉ ዋካዎች ናቸው” ሲል ምላሽ ሰጠኝ፡፡ የኮንሶ ማህበረሰብ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን “ጓድ መለሴ” ብሎ ነው የሚጠራቸው፡፡ በተለያዩ ንግግሮች እና መዝሙሮች ውስጥ በአፋኾንሶ “ጓድ መለሴ” የሚል ንግግር አዳምጫለሁ፡፡
በአጠቃላይ ባህላዊው የኮንሶ ከተሞች (ፓሌታዎች) በውስጣቸው የጋሞሌን መንደር በጐበኘሁበት ጊዜ ያየኋቸውንና ከላይ የገለጽኳቸውን ነገሮች አካትቷል። ባህላዊ ስልጣኔ ቀድሞ የገባውና ታታሪ ማህበረሰብ ለመሆኑ ምስክር ነኝ፡፡ ሆኖም እነዚህ ቦታዎች ይበልጥ በቱሪስቶች መጐብኘት ይቀራቸዋል፡፡ የደቡብ ክልል፣ የሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን እና የኮንሶ ወረዳ ይህን ድንቅ ተፈጥሮ በተሻለ ደረጃ ለቱሪስት አስጐብኝቶ ታታሪውን ህዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ ብዙ የቤት ስራ ይጠብቃቸዋል።
ምቹ የማረፊያ ሆቴሎች፣ የማይቋረጥ የሃይል አቅርቦት፣ የኢንተርኔትና የስልክ (የኔትወርክ) መሰረተ - ልማቶች በአግባቡ ከተዘረጉ እንደ ማሪያና አዶልፍ ያሉ የውጨ ቱሪስቶች ስድስት ቀን ብቻ ሳይሆን ስድስት ወር ለመቆየት ይገደዳሉ። የሚያስገድዳቸው ደግሞ የኮንሶ ተፈጥሮ ነው። “ኩርኩፋ የተሰኘው ከበቆሎና ከሞሪንጋ ቅጠል ተቀላቅሎ የሚሰራው ምግብ ስድስት ቀን ብቻ ሳይሆን ስድስት ወር በኮንሶ እንዲቆዩ የሚያስገድድ ነው፡፡ ለዚህ ነው በጽሑፌ መጀመሪያ “ኔትወርክ የለም እንጂ ኔትወርክ ቢኖር ከትሞ ኮንሶ ላይ መቀመጥ ነበር” የሚል ቅኔ ለመዝረፍ የዳዳኝ፡፡ ታዲያ ውቡን የኮንሶ ህዝብ መገለጫ ተፈጥሮዎች በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ከ15 ዓመት በላይ እልህ አስጨራሽ ትግል መደረጉን አቶ ገረሶ አጫውተውኛል፡፡  
የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ በራቆ በላቸው፤ የመብራት መቆራረጥና የኔትወርክ አለመኖር ትልቁ የካራት ከተማ ችግር መሆኑን አምነው፤ በቀጣይ ከዞኑና ከክልሉ ጋር በመነጋገር መፍትሄ ለማበጀት እየተጣረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ተዘዋውረን ያነጋገርናቸው የከተማዋ ነዋሪዎች በመብራት፣ በውሃና በዘይት ችግር መማረራቸውንና ስራ መስራት እንዳልቻሉ ገልፀው፤ በችግሮቹ ዙሪያ ህዝቡና አመራሩ በየጊዜው እየተሰባሰቡ ቢወያዩም ችግሩ እየባሰ እንጂ እየተሻለ እንዳልሄደ ተናግረዋል። በዚህ የተነሳ ነግደው ማትረፍና ኑሯቸው ማሸነፍ ስላልቻሉ መንግስት እልባት እንዲሰጥ ተማጽነዋል፡፡

Published in ህብረተሰብ
Saturday, 14 June 2014 12:04

የኢትዮጵያ ታሪክ

...በዚያም ወራት ደጃች ብሩ፤ ጭልጋ አርባ አምባ ታስሮ ሳለ፣ ሚሽቱ ወይዘሮ የውብዳር ከእልፍኝ አሽከሮቿ አንዱን መልምላ ውሽማ አበጅታ ነበረ፡፡ ይህን ነገር ደጃች ብሩ በሰማ ጊዜ አዘነ፡፡ በበገና እንዲህ ብሎ አለቀሰ፡፡ ...
“መከራን በሰው ላይ እንዲያ ሳቀለው፣
ምንኛ ከባድ ነው እኔ ብይዘው፡፡
መከራ ሲመጣ አይነግርም አዋጅ፣
ሲገሠግሥ አድሮ ቀን ይጥላል እንጅ፡፡
ዘሃው ሰለሰለ ሸማኔው ተቆጣ፣
እስተወዲያው ድረስ መጠቅለያ ታጣ፡፡
የኔታም አይመጡ እኔም አልመለስ፣
ዋ ቢቸና ቀረ እስተወዲያው ድረስ፡፡
ከእልፍኝ ሰው አይግባ ሚሽቴን ሰው አይያት አይሉም አይሉም፣
ፈረሱን ሰው አይጫነው፣ በቅዬን ሰው አይጫነው አይሉም አይሉም፣
ጠጁ ቀጠነብኝ፣ ሥጋው ጎፈየብኝ አይሉም አይሉም፣
ቀን የጣለ ለታ፣ የጨነቀ ለታ፣ ይደረጋል ሁሉም። አለ፡፡
የደጃች ብሩ ግጥም ብዙ ነው፡፡ በሰራው ክፋት ብድሩን ከፈለ፡፡ በዘመኑ ጎጃምን ሲገዛ ያደረገው ክፋት ተጽፎ አያልቅም፡፡ ሚሽቱ ወይዘሮ የውብዳር ቤተክርስቲያን ልትሳለም በምትወጣበት ቀን አስቀድሞ ሰው የገባ እንደሆነ የዱላ በረዶ ይወርድበት ነበር፡፡ በደረቤ በየወረዳው ፲ ፲ (አሥር አሥር) እንስራ ጉንዳን ለምስጥ ማጥፊያ ብሎ ደሃውን አስጨንቆት ነበረ፡፡ ያንን ጊዜ ባላገር ጉንዳን በሣምባ ሥጋ እየተሰለበ በእንስራ ውስጥ እየከተተ ወደ ሶማ አምባ ሲወስድ ጆሮውንና ትክሻውን እየነከሰ አስቸገረው፡፡ የዚህ ጊዜ በለቅሶ ሲአንጎራጉር እንዲህ አለ፡፡
ከመከራው ሁሉ የጉንዳኑ ባሰ፣
የተሸካሚውን ጆሮና ትክሻ እየተናከሰ፡፡ አለ፡፡
ደግሞ የሴት ብልት ጠጉር የበቅሎ ቁርበት ይበጃል ብሎ ፭፻ ጉንዲ ጠጉር በሚዛን አምጡ ብሎ በየወረዳው ጥሎ ደኃውን አስለቀሰው፡፡ በሚዛን ሳይሞላለት ጊዜ የራሱን ጠጉር እየጨመረ ቢሰጥ እምቢ እያለ ወርቅ ተገላገለው፡፡
ያን ጊዜ የሴት ዘመድ የሌለው ተቸግሮ ነበረ፡፡ ደግሞ አፄ ቴዎድሮስ እንዳይሰብረው ብሎ ሶማን ሊያሰራ ፴ ጎበዝ ግንድ ተሸክሞ ሲወጣ፣ ከጠባብ ቦታ ላይ ተጨናንቆ ግንዱ ወንጥሎት ገደል ይዞት ገባና አለቀ፡፡ ይኸን ደጃች ብሩ በሰማ ጊዜ ገበሬ ምንኛ ተዋዳጅ ነው፡፡ አንድነት ወርዶ አለቀ ወይ ብሎ ቀለደ፡፡ አለሚገባ እጁን  እግሩን የቆረጠው ሰውም ብዙ ነው፡፡
ይህን ሁሉ ክፋት ክርስቶስ መዝኖ ጊዜው ሲደርስ፣ በአጼ ቴዎድሮስ እጅ አግብቶ ሚሽቱን ለጠብደል ማላገጫ አድርጎ ሲአስለቅሰው ኖረ። የደጃች ብሩን ልቅሶ አጼ ቴዎድሮስ በሰማ ጊዜ ሎሌዎች በድለዋል አሉና ልቅጣዎ ብሎ ላከበት። ደጃች ብሩም ለጊዜው ኀዘን አብርትቶ ነበረና መንግሥትዎን ያሰንብትልኝ፡፡ ቃሉ ደረሰኝ፡፡ ግን የጮሁለት ሰው አለና የዚያን ቁርጥ ሳውቅ ይሁን አለ፡፡
መልክተኛው ከመድረሱ ውሽማዋን መብረቅ ገደለው፡፡ ደጃች ብሩም ክርስቶስ ሰማኝ፡፡ ፍርዱን ፈረደ፡፡ ባላጋራየ ሞተ ብሎ ላከ፡፡ አጼ ቴዎድሮስም ሰምቶ ተደነቀ፡፡ ለካስ ደጃች ብሩ አጥብቀው አዝነዋል፡፡ ክርስቶስም ሰማቸው፤ በኔም ቢአዝኑ ያደርሱብኛል ብሎ ፈተህ አምጣልኝ አለ፡፡
ከታሰረበት ፈትቶ ወደ አጼ ቴዎድሮስ እጅ ሊነሣ ሲኸድ፣ ያው ጋኔኑ ጥንተ ትቢቱ አልለቀው ብሎ ተከናንቦ ሎሚ ታህል ደንግያ በትከሻው ይዞ ሊታረቅ መጣ፡፡ አጼ ቴዎድሮስም ክንንቡንና የድንጋይቱን ማነስ አይቶ ተበሳጭቶ፣ ትቢትዎ አለቀቀዎምሳ ቢለው፣ ክንብንቤን እንደሆነ የጭልጋ በረሃ  ጠጉሬን ጨርሶት ባፍር ነው አለ፡፡ አጼ ቴዎድሮስም ከአብራጃው አገር መቅደላ ይቆዩ፡፡ እኔ ልፈታዎ ነበረ፡፡ ነገረ ክርስቶስ ማቆያ በትቢት ምክንያት አመጣብዎ፡፡ ፈቃዱ ሲሆን ይፈታሉ አለው፡፡  
ምንጭ - (አለቃ ተክለኢየሱስ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ፤ ሐተታ (በሥርግው ገላው (ዶ/ር))

Published in ባህል
Page 11 of 18