አንዲት የቆቅ ልጅ የስንዴ እሸት ትርክክ ብሎ በስሎ በሚገኝበት እርሻ አጠገብ ወጥመድ ተጠምዶ አይታ እናቷን “እናቴ ሆይ እሸት አምሮኝ ነበር፤ ከዚህ ማሣ ገብቼ እንዳልበላ ወጥመድ እንዳይዘኝ ሰጋሁ ምን ይሻለኛል?” ስትል ጠየቀቻት፡፡ እናቷም፤ “ተይ ልጄ ይቅርብሽ ትያዣለሽ አይሆንም” ብላ መከረቻት፡፡ ልጅቷ ግን “ግድየለሽም አይዙኝም ትንሽ ተክ ተክ አድርጌ ልውጣ” አለቻትና ገብታ ስትበላ ያ ወጥመድ እናቷ እንደፈራችው እግሯን ጥርቅም አድርጐ ያዛት፡፡ መቼም መከራ በመጣ ጊዜ በመጀመሪያ የሚታሰቡት ወላጆች ስለሆኑ፤ ያቺ የእናቷን ምክር አልሰማ ያለች ልጅ፤ “እናቴ ኧረ ተያዝኩልሽ” አለቻት፡፡ እናትየዋም፤ “ምነው ልጄ አስቀድሜ ነግሬሽ አልነበረም? አሁን ምን ላደርግልሽ እችላለሁ?” አለቻት፡፡

እማምዬ እባክሽ እርጂኝ? ፍቺልኝ ገመዱን?” “በምን እጄ?” “ታዲያ እንዴት ልሁን? ምን ይበጀኝ የኔ እናት?” “በዚህ ጊዜ እናት ለልጁዋ ምን ጊዜም ምክር አዋቂ ናትና፤ “ዝም ብለሽ የሞትሽ መስለሽ ተኝ” “ባለወጥመዱ ሲመጣ ሞታለች ብሎ ፈትቶ ይለቅሻል፡፡ ያኔ ታመልጫለሽ” አለቻት፡፡ ልጅ እንደተባለችው አደረገች፡፡

ባለወጥመዱ ሰው ሰብሉን ጐብኝቶ መጣና ቢመለከት ዝልፍልፍ ብላ ተኝታ ዐይኗን ጨፍና አገኛት፡፡ አጅሬ የሞተች መሰለውና “አዬ ጉድ ወጥመዴ ቆቅ ይዞልኝ ነበረ፡፡ ነገር ግን ሞተች” አለና አዘነ፡፡ ጓደኛው ከበላዩ ሰብል ይጠብቅ ነበርና “ወንድም” ብሎ ተጣራ “ወጥመዴ ቆቅ ይዞልኝ ነበረ፡፡ ነገር ግን በክታ አገኘኋት” ባልንጀራውም፤ እስቲ ወደላይ አጉናት” አለው ባለወጥመዱ ወደ ሰማይ ወርወር አደረጋት፡፡ ቆቋ ቱር ብላ ከጫካው ጥልቅ አለች፡፡

                                             * * *

ምክር መቀበልና ማክበር ይገባል፡፡ አደጋ ላይ ሊጥል የሚችልን ነገር አስቀድሞ ማሰብ፣ ማውጠንጠንና መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡ ብዙ አደጋዎችን፣ ብዙ ችግሮችን፣ ብዙ ውጣ - ውረዶችን ያየችው አገራችን መከራዋን ትወጣው እንጂ አብዛኛዎቹ የተከሰቱት ምክር በማይሰሙ መሪዎች፣ ኃላፊዎችና ሥራ አስኪያጆች ሳቢያ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ የታለፉ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ አጋጣሚዎች ደግመን ማጣት ከእንግዲህ ብርቱ ዋጋ ያስከፍለናልና ጥንቅቅ ብለን ማሰብ ይገባናል፡፡ የድህነት ነገር ሆኖብን ሁሌ ሥራችንን በዘመቻ እንድንሠራ እንገደዳለን፡፡ አንድን ሥራ በነጥብ መብራት አተኩረን መሥራት ትልቅ ጉልበት በማከማቸት ግብ እንድንመታ ይረዳናል፡፡ ሆኖም ዘላቂና የኔነት ስሜት ያለው ሥራ እንድንሠራ በሙያዊ ብቃት፣ በሥራ ክፍፍልና በሙሉ ስሜት እንድንራመድ ካልሆነ ለብዙ ችግር እንጋለጣለን፡፡ ጦርነትም ቢሆን እንኳ በኃይል በኃይሉ፣ በክህሎት በክህሎቱ ሲሰደር ነው ለግብ ይበቃል የሚባለው፡፡ የጋራ ጥቅም ላይ ያነጣጠሩ መስሎ የግል ጥቅምን በጐን ማሳደድ ሊነቃበት የሚገባ ጨዋታ ነው፡፡ “ሌላ ጊዜ አንቺ ይላል፤ ጠላ ስትጠምቅ እሜቴ ይላል” የሚለውን የወላይታ ተረት ከልብ ማስተዋል ዋና ነገር፡፡

መቼም የሀገራችን ነገር አንዱ ሲወርድ አንዱ ሲወጣ ያለበት ነው፡፡ ከሥራውም ይልቅ ሰውዬውን ለሚያይ ዘላቂነት ያለውና ያለፈውን ስህተት ለማረም የቻለ ጉዞ ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ የሠራተኛው፤ የፓርቲ አባሉ፣ የበታች ኃላፊው ሁሉ፣ ሁልጊዜ “እናቴን ያገባ ሁሉም አባቴ ነው” የሚልበት ዘመን ያከተመ ይመስላል፡፡ “ተሰናባች አይርገምህ፤ ተተኪው አይጥላህ” የሚለውን በጥንቃቄ ካዩት ትርጉም ያለው ቁምነገር ያስጨብጠናል። ተሰናባች በግፍ፣ በምቀኝነት ወይም በአድልዎ ተባሮ ከሆነ እርግማኑ ይደርስብኛል ብሎ ማሰብ የአባት ነው፡፡ ተተኪው በተንጋደደ ዐይን የሚያይ ከሆነና “ለዚያኛው ያልተኛ እኔን አይምረኝም” ብሎ ያሰበ ከሆነም ሲሰጉ መኖር ነው፡፡ ከዚህም ይሰውረን፡፡

የሚመጣውን ሁሉ ተዘጋጅቶ መጠበቅ ያለ ነው፡፡ ጣር መጣ ጦር መጣ እያሉ በጣም ያስፈራሩት ጀግና፤ በዝግታ እየተዘጋጀ፤ “ይምጣ ከመጣ ሞቼ ልጠብቀው እንዴ ልዘጋጅ እንጂ!!” አለ የሚባለውንም አንዘንጋ፡፡ ጉዳዩን የሚያቅ፤ የበሰለ፣ ባለገድልና ባለታሪክ ሰዋችንን አንናቅ፡፡ ከየቦታው ሰብስበን ሥራ ላይ እንዲቀመጥ እናድርግ፡፡ ልታይ ልታይ የሚለውንና የአደባባይ ጌጥ የሆነውን ትተን፤ ከልቡ ለሀገር የሚያስበውን እናስተውል፡፡ “ይቺ እንዴ ትጨፍራለች?” ቢባል፤ “ልብስ አጥታ እቤት የቀረችውን ባየህ!” አለ፤ የሚባለው የወላይታ ተረት የሚነግረን ይሄንኑ ነው፡፡

Published in ርዕሰ አንቀፅ

                       ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በአገር አቀፍ ደረጃ እየተከበረ የሚገኘውን “የፍትህ ሳምንት” ምክንያት በማድረግ የተለያዩ የህግ ባለሙያዎችን የፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታን ጨምሮ የተለያዩ የፍትህ አካላትን ሃላፊዎች እንዲሁም የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች አነጋግረናል - በፍትህ ዙሪያ፡፡ “የህግ የበላይነት ለመልካም አስተዳደር መስፈን በህዝቦች ተሳትፎ” በሚል መሪ ቃል የፍትህ ሚኒስቴር፣ የፌደራል ፍርድ ቤቶች፣የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ፣የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በጋራ በመሆን ባዘጋጁት “የፍትህ ሳምንት” ላይ ጥናቶች ቀርበው ውይይቶችም ተካሂደዋል፡፡ ለመሆኑ የፍትህ ሳምንት መከበር ፋይዳው ምንድነው? በአገሪቱ ላይ ያለው የፍትህ ሁኔታስ ምን ይመስላል? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ሰላም ገረመው ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ወገኖች ያሰባሰበቻቸው አስተያየቶች እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

“ውሳኔ ለማግኘት ሁለት አመት ድረስ ሊቆይ ይችላል”
የወንጀል ጉዳዮች ቶሎ አይወሰኑም፡፡ የፍትህ ስርአቱ ጥሩ አይደለም፡፡ የተወሰኑ ችሎቶች ላይ ከባድ የሚባሉ ችግሮች አሉ፡፡ 16ኛ የወንጀል ችሎት፣ 3ኛ የወንጀል ችሎትና ጠቅላይ ፍ/ቤት የፍትሃብሔር ችሎት አንድ በመሆኑ ከፍተኛ ችግር ይታይባቸዋል፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ደግሞ 7ኛ እና 11ኛ ችሎት አብዛኛውን ጊዜ አዳዲስ ሰዎች ስለሚመጡ ጉዳያችን ቶሎ አያልቅም፣ ውሳኔ ለማግኘት ሁለት አመት ድረስ ሊቆይ ይችላል፡፡ አቃቤ ህጐች ደግሞ ችግራቸው ክሶችን ቶሎ አይከፍቱም፡፡
አቶ ስሜነህ ታደሰ
(ጠበቃ)

“ፍትህ የሚከበር ሳይሆን የሚሰፍን ጉዳይ ነው”
የፍትህ ሳምንት መከበር ሳይሆን የሚያስፈልገው መበየን ነው ያለበት፡፡ ፍትህ የፈጣሪ ስራ ነው፡፡ ፍትህ የሚከበር ሳይሆን የሚሰፍን፣ የሚተገበር ጉዳይ ነው፡፡ ህጋዊነት ማስፈን ትንሽ ስራ ቢሆንም ለአገራችን ግን ህጉን አክብሮ መስራት በራሱ በቂ ነበር፡፡ ፍትህ የአንድ አገር ትልቅ ጉዳይ ነው፡፡ ማርኬሌሊ የተባለ የጣሊያን የፖለቲካ ፈላስፋ ሲናገር፤ “አንዳንዴ ሰዎች የምትናገረውን እንጂ የምትሠራውን አያዩም” ይላል፡፡ ስለ ፍትህ ስትናገሪ ስራሽን ያላዩ በንግግር እንዲታለሉ ለማድረግ ካልሆነ በስተቀር ሌላ ጥቅም የለውም፡፡ በእኔ ደንበኞች ላይ እየሆነ ያለው ነገር ይሄ ነው፡፡ ተጠርጣሪዎች ቶርች ተደርገው (ተገርፈውና ተደብድበው) በኢቴቪ አለአግባብ እንዲናገሩ እየተደረገና ከዚያም በዚህ ጉዳይ ላይ የፍትሀብሔር ክስ ለመመስረት ስንጠይቅ ፍ/ቤቱ ለመጀመሪያ ጊዜ አልቀበልም ብሏል፡፡ እንግዲህ “ፍ/ቤት ለሁሉም እኩል ነው” ተብሎ ነው የሚታሰበው፡፡ ግን ፍ/ቤት ራሱ ህግን ሳያከብር የፍትህ ሳምንት ማክበር ምን ይጠቅማል? በቶርች ማስረጃ ለማውጣት ሰው እየተሰቃየ ነው፡፡ የፀረ ሽብር አዋጁን ተቃውመን ለመንግስት አጣሪ ጉባኤ ጥያቄ ብናቀርብም እስካሁን ምላሽ አላገኘንም፡፡ የትላንት ባለስልጣናት ዛሬ ታስረው መብታችን ተጣሰ እያሉ በመጮህ ላይ ናቸው፡፡ ይሄን ሁሉ ስናይ በኢትዮጵያ ያለው ፍትህ የሚያስታውሰን የጣሊያኑን ፈላስፋ አባባል ብቻ ነው፡፡
አቶ ተማም አባቡልጎ
(ጠበቃ)

“ፖሊስ ተጠርጣሪዎችን ከያዘ በኋላ ማስረጃ መፈለግ የለበትም”
ፍ/ቤቶች ኮምፒዩተራይዝድ መሆናቸው ጥሩ ነገር ነው፡፡ በየቦታው ባሉ ህንፃዎች ላይ ፍርድ ቤቶች መከፈታቸው አንድ ለውጥ ነው፡፡ ፖሊስ ከአቃቤ ህግ ጋር መስራቱ፣ ክሱን ለመመስረት በአንድ ቦታ ስለሆኑ ጊዜን ያቆጥባል፤ በፊት የተለያየ ቦታ ስለሆኑ ክስ ለመመስረት ብዙ ጊዜ ይፈጅ ነበር፡፡ የፖሊስ ማስረጃ ፍለጋ ኋላቀር መሆን ግን አሁንም መስተካከል ይቀረዋል፡፡ ብዙ ጊዜ ተከሳሽን አስሮ “ምርመራ ይቀረናል” እያለ በወንጀል ጉዳይ የተጠረጠሩትን ያጉላላል፡፡ ታሳሪና ጠበቃ በዋናነት መገናኘት ያለባቸው በምርመራ ጊዜ ቢሆንም ፖሊስ ግን ምርመራ ሳልጨርስ ተከሳሽና ጠበቃን አላገናኝም ይላል፡፡ እንደውም ተከሳሽ ቃሉን ሊሰጥ የሚገባው ጠበቃው ባለበት ሁኔታ መሆኑን ህግም ይደግፋል፡፡ ሌላው ቢቀር ተከሳሽ ቃሉን ያለመስጠት መብት እንዳለው እየታወቀ፣ ከጠበቃው ጋር እንዳይገናኝ መደረጉ አግባብ አይደለም፡፡ ፖሊሶች ጋ ያለው የተሳሳተ አመለካከት፣ ጠበቆችን ፍትህ የሚያዛቡ አድርጐ ማየት ነው፡፡ አንድ ተከሳሽ በምርመራው ጊዜ ተገቢውን እርዳታ ካላገኘ፣ መደበኛ ክስ ሲከፈት በጣም አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡ ሌላው በወንጀል ጉዳይ የተጠረጠሩ ሰዎች ቶሎ ፍ/ቤት መቅረብ አለባቸው ፤ ፖሊስም ቢሆን መጀመሪያ ማስረጃ መያዝ አለበት እንጂ ተጠርጣሪዎችን ከያዘ በኋላ ማስረጃ መፈለግ የለበትም፡፡
አቶ ደበበ ኃ/ገብርኤል
(የህግ ባለሙያ)

“የፍትህ ስርዓቱ ብዙ ይቀረዋል”
የፍትህ ሳምንት መከበሩ ምን ይጠቅማል? ምናልባት የሚመለከታቸው ተገናኝተው ችግሮችን ለመቅረፍ ከሆነ ያስኬዳል፡፡ ዳኞችና አቃቤ ህጐች አብረው ሊበሉና ሊጠጡ ከሆነ ግን ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አያስቸግርም፡፡ በአንድ በኩል ጥሩ ነገር አለው፤ በሌላ በኩል ችግር አለው፡፡ የአገራችን የፍትህ ስርአት ብዙ ይቀረዋል - ከአወቃቀር፣ ከአደረጃጀት፣ ከብቃት፣ ከሰው ሃይል ጀምሮ … የህግ እውቀት ማነስ ችግሮች ሁሉ አሉ፡፡ የፌደራል ፍ/ቤቶች በቤኒሻንጉል፣ በሱማሌ፣ በአፋር፣ በደቡብ እንዲቋቋሙ በአዋጅ የወጣው በ1995 ዓ.ም ነው፤ እስካሁን ግን አልተቋቋመም፡፡ ይሄ የሚያሳየው ተደራሽ አለመሆናቸውን ነው፡፡ የፌደራል አቃቤ ህጐችም በመላው ክልል ነው መቋቋም ያለባቸው፡፡ አሁን ያለው አዲስ አበባ እና ድሬደዋ ላይ ብቻ ነው፡፡
ዘርአይ ወ/ሰንበት
(የቀድሞ አቃቤ ህግ)

“የፍትህ ሳምንት ማክበር ማሾፍ ነው”
ፍትህ በሌለበት አገር የፍትህ ሳምንት ማክበር መቀለድ ነው የሚሆነው፡፡ ፍትህ ያጣ ህዝብ እያለቀሰ፣ ፖለቲከኛና ተቃዋሚ ስለሆኑ ብቻ ዜጐች እየታሰሩ፣ ሰዎች ከሃይማኖታቸው ጋር በተያያዘ “ሽብርተኛ” ተብለው እስር ቤት እየገቡ፣ ከዛም አልፎ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ተነፍጐ ጋዜጠኞች በሚታሰሩባትና አሁንም ድረስ “አምላክ ይፈርዳል” በሚባልባት አገር የፍትህ ሳምንት ማክበር ማሾፍ ነው፡፡ ፍትህ መታየት ያለበት በተግባር ነው፡፡ ባለፈው አመት ኪሊማንጀሮ የተባለ የጥናት ተቋም ባወጣው ሪፖርት፤ በኢትዮጵያ ውስጥ እምነት ከማይጣልባቸው ተቋማት አንዱ የፍትህ አካላት መሆናቸው ተገልጿል፡፡
ለምሳሌ አንዷለም አራጌን በእስር ቤት መጠየቅ አይቻልም፡፡ ከፍርድ ቤት ውሳኔ በፊት ኢቴቪ ተጠርጣሪዎችን “ሽብርተኛ” እያለ የሚፈርድበት ጊዜ አለ፡፡ በማረሚያ ቤት ደግሞ ድብደባ፣ ማንገላታት፣ ጨለማ ቤት ማሰር--- አለ፡፡ ታዲያ እዚህች አገር ላይ ነው የፍትህ ሳምንት የሚከበረው? ፍትህ የሚባለውን የምናውቀው በስም ነው፡፡
አቶ ዳንኤል ተፈራ
(የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ)

“እዚህ አገር ይግባኝ የሚባለው ለእግዚአብሔር ነው”
የፍትህ ስርአቱ የተጠናከረ ነው፤ የኢህአዴግን ፖለቲካ እንዲያገለግል የተቀመጠ ነው፡፡ እንዲህ የምንለው የፍትህ ስርአቱን ደጋግመን በሞከርነው ነገር ስላየነው እንጂ ኢህአዴግን ስለምንጠላው አይደለም፡፡ ውሳኔዎቹ ፖለቲካዊ ናቸው፡፡ በቅርቡ እኛ ላይ የደረሰ የፍትህ መስተጓጎል አለ፡፡ የወረዳ ፓርቲ ሃላፊ የሆነ ግለሰብ የአባትህን መሬት አታርስም በሚል ፍ/ቤት ተከሶና ተፈርዶበት ሆሳእና ታስሮ ነው ያለው፡፡ ማስረጃ የማይሰማ ፍ/ቤት ባለበት ሁኔታ የፍትህ ሳምንት ማክበር ጨዋታ ነው፡
እኛ ራሳችን የአገራዊ ምርጫ ጉዳይ ህገወጥ ነው ብለን የተቃጠለውንና መፀዳጃ ቤት የተወረወረውን ድምፅ የተሰጠበትን ወረቀት ሰብስበን ስንሄድ “በእለቱ ነው ክስ መመስረት የነበረባችሁ” ተባልን፡፡ በእለቱ እንዳንሄድ እሁድ ነበር፤ እነሱ ግን እሁድም እንሠራ ነበር አሉ፡፡ ይሄንን ደግሞ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ አያውቅም፡፡ ስለዚህ ይሄ የፍትህ ሳምንት ሽፋን ነው እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ እዚህ አገር ይግባኝ የሚባለው ለእግዚአብሔር ነው፡፡
ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ
(የመድረክ ፓርቲ ም/ሊቀመንበር እና
የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ)

“መንግስት ችግሩን አሳምሮ ያውቃል”
በአፍሪካ ደረጃ በተደረገ ጥናት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ እምነት የማይጣልባቸው ተቋማት ከተባሉት አንዱ የፍትህ ስርአት መሆኑ ተገልጿል፡፡ ዜጐች መፍትሔ እያጡ ነው፡፡ ፍትህ ማጣታቸው ገዝፎ እየታየ የመጣው ከአፄው ጀምሮ ነው፡፡ የፍትህ ሳምንት መከበሩም ከፕሮፖጋንዳ ያለፈ ነገር አለው ማለት አይቻልም፡፡ መንግስት ችግሩን አሳምሮ ያውቃል፡፡ ለፍትህ መጥፋቱ ዋናው እኮ የስልጣን ክፍፍል አለመኖሩ ነው፡፡ የአስፈፃሚው አካል እንደልቡ ተንቀሳቅሶ መስራት ካልቻለ ፍትህ ይዛባል፡፡
ዶ/ር መረራ ጉዲና (የመድረክ ፓርቲ ም/ሊቀመንበር)
“ፍትህን ለማስፈን በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል”
ይቅርታ ለጠየቁ ታራሚዎች ሁሉ ይቅርታ ይሰጣል ማለት አይደለም፡፡ በሀገራችን ህግ እንደ መብት አልተቀመጠም፡፡ ይቅርታ ሰጪው አካል በተለያዩ ምክንያቶች ይቅርታ ሊሰጣቸው ይገባል ብሎ ለሚያስባቸው ወገኖች ይቅርታ ይፈቅዳል፡፡ እነዚህ ሰዎች ባለው አግባብ ይቅርታቸውን አቅርበው እንዲታይላቸው ማድረግ ይችላሉ፡፡ ጠይቀው ካልተፈቀደላቸው ደግሞ ከስድስት ወር በኋላ መልሰው የመጠየቅ መብት አላቸው፡፡ ይህንን ሚኒስትሩ ሲመጡ የሚወስኑት ይሆናል፡፡
በአገሪቱ ፍትህን ለማስፈን በተወሰዱ እርምጃዎች በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ የፍትህ አካሉን የባለሙያዎች ህገመንግስታዊ አመለካከቶች ለማረጋገጥና አቅማቸውን ለማጐልበት በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ የፍትህ ሳምንት የሚከበረው በቀጣይ ፍትህ በማስፈን ረገድ ምን ሊከናወን እንደሚችል ለማየት እንዲሁም እስካሁን የተሰሩ ስራዎችን በመገምገም ችግሮችን ለመቅረፍ ሲሆን ህዝቡ የፍትህ ስርአት ባለቤት በመሆኑ የአገራችንን የፍትህ ሁኔታ ለማሳየትም ጭምር ነው፡፡
አቶ ልዑል ካህሳይ
(የፍትህ ሚኒስቴር፤ ሚኒስትር ዴኤታ)

“ህብረተሰቡ ካላገዘን ውጤታማ አንሆንም”
ሙስና መኖሩ በአደባባይ የሚታይ ነገር ነው፡፡ ይሄንን ለእናንተ የሚናገሩ ሰዎች ለእኛም መጥተው መንገር አለባቸው፤ እንጂ በአደባባይ “ፍ/ቤት ውስጥ ሙስና ይሰራል” ብሎ ብቻ ማውራት አይጠቅምም፤ በእርግጥ ሙስና የሚሰሩ የሉም አንልም፡፡ ከዳኝነት አካላት ብቻ ሳይሆን ከታችም ያሉ ሰዎች ሊፈፀሙት ይችላል፡፡ በዳኛም ስም የሚፈፀም ይሆናል፤ የተወሰኑ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡
“ለዳኛ ብር እንሰጣለን” የሚሉ በርካታ ስራ ፈት ፍ/ቤት የሚውሉ ሰዎች እንዳሉ እንሰማለን፤ ግን ህብረተሰቡ ካላገዘን ውጤታማ አንሆንም፡፡ በዚህ ምክንያት ተቋሙ ተአማኝነት ያጣል፡፡ በጥቂት ሰዎች አላስፈላጊ ስራ ተቋሙ መወሰን የለበትም፡፡ በሙስና ብቻ ሳይሆን በሌላም ሊሆን ይችላል፡፡ ዳኞች ቢሆኑም ያደረጉት ከሆነ ውሳኔ እንሰጣለን፡፡ መረጃ በሌለበት ሁኔታ ግን ዳኝነት በነፃነት የሚታይ ነገር በመሆኑ ያለአግባብ መጠየቅ አንችልም፡፡ በተለይ ደግሞ እንዲህ አይነት መድረኮች መዘጋጀታቸው ከህብረተሰቡ ጋር በቅርበት በመገናኘት ችግሮችን ለመፍታት ያስችላል፡፡
የተከበሩ አቶ ተገኔ ጌታነህ
(የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት)

“በታራሚዎች አያያዝ በርካታ መሻሻሎች አሉ”
የታራሚዎችን መብት ለማስከበር ከህገመንግስቱ ጀምሮ ለጠባቂዎቻችን ስልጠና እንሰጣለን፡፡ በእኛ ብቻ ሳይሆን ከሰብአዊ መብት ጋር ተነጋግረን ስልጠናውን እንዲያገኙ እናደርጋለን፡፡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ድርጅት በአንድ ወቅት ያደረገውን ጥናት ይፋ አድርጐ ነበር፡፡ በዚያ መነሻነት በዝርዝር እቅድ አውጥተን ግምገማ አድርገናል፡፡ ከእኛ ባለፈ ደግሞ ፓርላማ በየ6 ወሩ ይገመግመናል፡፡ አቅም በፈቀደ መንገድ ስራዎች ይከናወናሉ፡፡ ከህጉ ውጭ በታራሚዎች ሰብአዊ መብት ላይ ችግር የሚፈጥር ካለ አስተዳደራዊ እርምጃ እንወስዳለን፤ የወሰድንባቸውም አሉ፡፡ እነዚህን ሁሉ አድርገን በግለሰብ ደረጃ የሚፈፀሙ ጥፋቶች የሉም ማለት ግን አይደለም፤ በርካታ ታራሚዎች ስላሉ ችግር መከሰቱ አይቀርም ፤ነገር ግን በርካታ መሻሻሎች አሉ፡፡
አምስቱ ተቋማት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድን መነሻ በማድረግ የጋራ ስትራቴጂክ እቅድ አዘጋጅተዋል፡፡ እነዚህ እቅዶችም እያንዳንዱ ተቋም ከራሱ ተጨባጭ ሁኔታ ተነስቶ ወደ እራሱ እየወሰደ የሚሠራበት እና በጋራ የሚሰሩ ስራዎችም ለማከናወን በአጠቃላይ በፍትህ ስርአት ውስጥ ያሉትን ክፍተቶች አይቶ በመነጋገር፤ የአሰራር ክፍተቶች ካሉ በመመልከትና በመቅረፍ ትኩረት ሰጥተን እየሰራናቸው ነው፡፡ ማረሚያ ቤትን ብንወስድ ከፍ/ቤት ጋር የሚያገናኙ ስራዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ዝዋይ የታሰረ ታራሚ በቀጠሮ ጊዜ ወደዚህ በመምጣት ከሚንገላታ በፕላዛ ቲቪ በቀጥታ የፍ/ቤቱን ጉዳይ እንዲከታተል የሚደረግበት አሠራር ዘርግተናል፡፡ የአመክሮና የይቅርታ አሠራር ሁኔታንም በተመለከተ ታራሚ እንዳይጉላላ ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እነዚህን ሁኔታዎች እየሰራን ሲሆን ጥምረታችን ደግሞ ይሄንን ለማከናወን ያግዛል፡፡
የፍትህ ሳምንት መከበሩ ጥቅም አለው፡፡ ስራችን ከህዝብ ውጭ አይደለም፤ እኛ ጥሩ ሰራን ብንልም በህዝብ ዘንድ ደግም እርካታን ያልፈጠሩ ነገሮች ይኖራሉ፡፡ እነዚህን ከህዝብ ጋር ተገናኝተን ለመወያየት እድል ይሰጠናል፡፡ ሁለተኛ የተቋማችንን ገጽታ ከመገንባት አንፃርም ትልቅ ድርሻ አለው፡፡
አቶ አብዱ ሙመድ
(የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ዋና ዳሬክተር)

“ህገመንግስቱን በማክበር እየሰራን ነው”
በሙስና ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች ፍ/ቤት ቀርበው የሰብአዊ መብት ጥሰት ተፈፀመብን ሊሉ ይችላሉ፣ ግን በማስረጃ አላረጋገጡም፡፡ የምርመራ ስርአታችን ህግን የተከተለ ነው፤ በተቻለ መጠን እኛ ጋ የምንመረምራቸው ወንጀሎች በአገርና በህዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳሉ ተብለው የሚታሰቡትን ነው፡፡ እነዚህ ወንጀሎች የተለያዩ ግብአቶች ይኖራቸዋል፡፡ ተጠርጥረው የሚመጡት ደግሞ ንፁህ ሊሆን ይችላል ወይም ሊወሰንበት ይችላል፡፡ እኛ ጋ ደግሞ ይህንን ሁለቱንም በማየት ነው ምርመራ የምናደርገው፡፡ በምርመራችን ድርጊቱ ለመፈፀሙ በቂ ማስረጃ ካለን፣ ፈፃሚው ማነው? የመፈፀም ደረጃው ምንድነው? የሚለውን ማግኘት፣ መፈፀሙ ጥርጣሬ ካለው ማረጋገጥ፣ የፈፀመው ሌላ አካል ከሆነ እኛ ጋር በተጠርጣሪነት ያለውን ግለሰብ ነፃነት አረጋግጠን እንሸኛለን፡፡
ከዚያ አኳያ ሳይንሳዊ ምርመራዎች የምርመራ ህጐች የሚፈቅዳቸው አርትንም ጭምር ሁሉ እንጠቀማለን፤ መርማሪዎቻችን የካበተ ልምድ አሏቸው፡፡ በሽብር በተደራጁ፣ በሙስና ወንጀሎች፣ በፋይናንስ ወንጀሎች ጥሩ ውጤቶች አሏቸው፡፡ ከፍተኞች ለጀማሪዎች እነዚህን ልምዶቻቸውን የሚያስተላልፉበት እና አዳዲሶችም የተሻለ ነገር ለማድረግ የሚጥሩበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ በዚህ ሂደት በባህሪያቸው ብልጣ ብልጥ የሆኑና የማጭበርበር ባህሪ ያላቸው ፍ/ቤትን ለማሳሳት ይፈልጋሉ፡፡ የምርመራ መነሻ ላይ የመጀመሪያ ጥያቄ የዋስትና መብት፣ የዘመድ፣ የጠበቃ፣ የሃይማኖት፣ የመጠየቅ መብት ተከለከልን ነው፡፡ ሁለተኛው ነገር በምርመራ ሂደት እንዲህ ተደረግን፣ ሰብአዊ መብታችን ተጣሰ የሚሉ ነገሮች ናቸው፡፡ እኛ ግን ምርመራዎቻችንን የምናካሂደው ተጨባጭ በሆኑ ነገሮች ላይ ተጠቅመን ነው፡፡
በየደረጃው ያለን ሃላፊዎች የሚደረጉትን ምርመራዎች የምናይበት ሁኔታ አለ፡፡ ፍ/ቤት ባለው በማንኛውም ጥርጣሬ ላይ እውነቱን ማረጋገጥ ይችላል፡፡ የሰብአዊ መብት ቅሬታም ሲቀርብለት እኛን መጥቶ ማየት ይችላል፤ እኛም ህገመንግስቱን በማክበር እየሰራን ነው፡፡ተጠርጣሪዎቹ ያነሷቸው ነገሮች እንዳይፈፀሙ ከፍተኛ ጥረት ይደረጋል፡፡ በትላልቅ ወንጀሎች አንዳንድ ሰዎች እንዲህ አይነት ነገር ቢያነሱም የምርመራ ጊዜያቸውን ጨርሰው ማረሚያ ቤት ሲሄዱ የምርመራውን ሂደት ሲኮንኑ አይታዩም፡፡ ስለዚህ እንደ ህዝብ ሰብአዊ መብቱ ተጥሷል አልተጣሰም የሚለውን መገመት ይቻላል፡፡ ይሄ ዘዴ ክሱ ሲመሰረት መጀመሪያ ለማምለጥ የሚያደርጉት ቀላሉ ዘዴያቸው ነው፡፡
የፍትህ ሳምንት ዋና አላማው፣ የፍትህ አገልግሎት የምንሰጥ ተቋማት እና በቀጥታ አገልግሎት ተጠቃሚ የሆነው ህብረተሰብ እና ባለድርሻ አካላትን በፍትህ አሰጣጥ ዙሪያ ልዩ ትኩረት ሰጥተን እንድንወያይ ማድረግ እና ጥሩ አፈፃፀሞቻችንን ማጉላት፣ ደካማ አፈፃፀሞቻችንን ማሻሻል የምንችልበትን ውይይት እና ምክክር የምናደርግበት መድረክ ነው፡፡
ም/ኮሚሽነር ጀነራል መስፍን አበበ (የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዘርፍ ሃላፊ)

 

  • በሌሊት እርቃኔን ሆኜ ቀዝቅዛ ውሃ እየተደፋብኝ ምርመራ ይካሄድብኛል” - ወ/ሮ አልማዝ
  • “የተቋሙን ስም ለማጉደፍ የታሰበ የሃሰት አቤቱታ ነው” - ፀረ ሙስና ኮሚሽን

የፀረ ሙስና ኮሚሽን ባለፈው ወር ወደ ፍ/ቤት ባቀረባቸው ተጠርጣሪዎች ላይ የጀመረውን ምርመራ እንዳላጠናቀቀ በመግለፁ፤ ለሦስተኛ ጊዜ የ14 ቀናት ቀጠሮ ተፈቅዶለት ተጠርጣሪዎች በእስር እንዲቆዩ ታዘዘ፡፡ በአምስት የምርመራ መዝገቦች የተካተቱት ከአርባ በላይ ተጠርጣሪዎች ሰሞኑን እንደገና ፍ/ቤት የቀረቡ ሲሆን፤ ከተጠርጣሪዎች አንዷ የሆኑት ወ/ሮ አልማዝ ከበደ በውድቅት ሌሊት ራቁታቸውን ቀዝቃዛ ውሃ የተደፋባቸው ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑን ለፍ/ቤቱ ገልፀዋል፡፡ ፍ/ቤቱ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በተለያዩ መዝገቦች የቀረቡት ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ ነጋዴዎች፣ ትራንዚተሮችና ደላላዎች እንዲሁም የገቢዎችና ጉምሩክ ሠራተኞች የጠየቁትን የዋስትና መብት በመከልከል የምርመራ ቡዱኑና አቃቤ ህግ ለ3ኛ ጊዜ የጠየቁትን የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ፈቅዷል፡፡ ሁሉም ተጠርጣሪዎች በጠበቆቻቸው ለፍ/ቤቱ ባቀረቡት አቤቱታ፣ ፀረ ሙስና ኮሚሽን ካሁን በፊት ተጠርጣሪዎቹን የያዝኳቸው በበቂ ማስረጃ ነው ማለቱን ጠቅሰው፣ ምርመራዬን አልጨረስኩም እያለ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ መጠየቅ አልነበረበትም ብለዋል፡፡

የፀረ ሙስና ኮሚሽን ሁለቴ የ14 ቀን የቀጠሮ እንደተሰጠው የተጠርጣሪ ጠበቆች ገልፀው፤ ኮሚሽኑ ምርመራዬን አላጠናቀቅኩም ብሎ እንደገና ጊዜ ይሰጠኝ ማለቱ ስራውን በትጋት እየተወጣ አለመሆኑን ያመለክታል ብለዋል፡፡ የፀረ ሙስና ኮሚሽን መርማሪ ቡድን በበኩሉ፣ እስካሁን ያከናወናቸውን ስራዎች ለፍርድ ቤቱ ሲዘረዝር በተጠርጣሪዎች መኖሪያ ቤትና ቢሮ በብርበራ የተገኙ ሠነዶችን ሲያጣራ መቆየቱን ጠቅሶ፣ ዲጂታል ማስረጃዎችን ለሙያተኛ በመላክ ውጤቱን እየተጠባበቀ መሆኑን ገልጿል፡፡ ከአዲስ አበባ ውጪ በሞጆ፣ በአዳማ፣ በሚሌ እና በአዋሽ የገቢዎችና የጉምሩክ ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶች የምርመራ ቡድን ተልኮ ምርመራ እያከናወነ መሆኑን ለፍ/ቤት ተናግሯል፡፡ ቀረጥ ሰውረዋል ተብለው በተጠረጠሩት ድርጅቶች ላይ የተጀመረው የኦዲት ስራ አለመጠናቀቁን የገለፀው ኮሚሽኑ፤ ስራው ከተጠናቀቀ በኋላ የኦዲተሮችን ቃል እቀበላለሁ ብሏል፡፡

ምንጩ ያልታወቀ ሃብትን ህጋዊ አስመስሎ ከመያዝ ጋር በተገናኘ የተጀመሩ ምርመራዎችም እንዳልተጠናቀቁ ኮሚሽኑ ገልፆ፤ ፍ/ቤቱ የምርመራውን ስፋት እና ውስብስብነት በማገናዘብ የ14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ይፍቀድልኝ ሲል ጠይቋል፡፡ ፍ/ቤቱም ግራ ቀኙን አይቶ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ፈቅዷል፡፡ ካሁን በፊት በርካታ ተጠርጣሪዎች የተለያዩ በደሎች እና ድብደባ ጭምር እየተፈፀመባቸው መሆኑን በመግለፃቸው ጉዳያቸው እንዲመረመር በፍርድ ቤት የተሰጡ ትዕዛዞች የት እንደደረሱ ባይታወቅም፣ በዚህ ሳምንትም ከተጠርጣሪ ለቀረበ ተመሳሳይ አቤቱታ ተመሳሳይ የምርመራ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡ ከተጠርጣሪዎች አንዱ የሆኑት ወሮ አልማዝ ከበደ፣ በምርመራ ወቅት ሰብአዊ ክብራቸውን የሚነካ ነገር እየተፈፀመባቸው መሆኑን ለፍርድ ቤቱ ገልፀው፣ ከምሽቱ 6 ሰዓት ራቁታቸውን ቀዝቃዛ ውሃ እየተደፋባቸው ምርመራ እንደሚካሄድባቸው ተናግረዋል፡፡ ወ/ሮ አልማዝ አቤቱታቸውን ለፍርድ ቤቱ ሲያቀርቡ ቤተሰቦቻቸው ያለቀሱ ሲሆን፤ የፀረ ሙስና ኮሚሽን የምርመራ ቡድን ድርጊቱን ተቃውሟል፡፡ ተጠርጣሪዎች ያቀረቡት አቤቱታ “ሃሰት ነው” ሲል ተቃውሞ ያሰማው የፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ የተጠርጣሪዋ አቤቱታ የተቋሙን ስም ለማጉደፍ ታስቦ ቤተሰቦቻቸው ጭምር የተሣተፉበት በምክክር የተደረገ ነው ብሏል፡፡ በሌላ ትዕዛዝም የህክምና እና ከሰብአዊ መብት ጥሰት ጋር ተያይዘው ከተጠርጣሪዎች የቀረቡ አቤቱታዎችን በተመለከተ የኮሚሽኑ የምርመራ ቡድን እንዲያጣራና ክትትል እንዲያደርግ ፍርድ ቤቱ ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡

Published in ዜና

                           አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) መንግስትና ገዢው ፓርቲ የአገሪቷን ሁሉንም ነገር ለፖለቲካ ፍጆታ መጠቀማቸው አገርን አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ ሊቆም እንደሚገባ ገለፀ፡፡ ከትላንት በስቲያ ፓርቲው በፅ/ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ “የኢህአዴግን ስርዓት ከቀደሙት አምባገነን ስርዓቶች ለየት የሚያደርገው ሁሉንም ነገር ለፖለቲካ ስልጣን መጠቀሚያ ማዋሉ ነው” ያለው አንድነት፤ ከዚህም ውስጥ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ አንዱ እንደሆነ ገልፃል፡፡ ግድቡ ከመጀመሩ በፊት ማለቅ የነበረባቸው ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ነበሩ፣ ግድቡን ከፓርቲ አጀንዳ ወደ ህዝብ አጀንዳነት ማውረድ አለበት፣ የግድቡ ስራ አንድ አካል የሆነውን የወንዝ አቅጣጫ ማስቀየር በግንቦት ሀያ ዕለት ማድረጉ ፖለቲካዊ እንጂ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የለውም፣ ያለው አንድነት ፓርቲ፤ መንግስት ለግድቡ ግንባታ ከጉሮሮው እየነጠቀ የሚወስደው ከህዝብ ስለሆነ የአባይ ግድብ ጉዳይ የህዝብ አጀንዳ እንዲሆን መንግስት ከተቃዋሚዎችም ሆነ ከሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ጋር አገራዊ ውይይና መግባባት ላይ መድረስ እንዳለበት ፓርቲው በመግለጫው አሳስቧል፡፡

“የአንድ መንግስት ግዴታዎች የሆኑት ተግባራት መንገድ ውሃ፣መብራትና መሰል ተግባራት መዳረሻቸው የፖለቲካ ስልጣን ማራዘም ነው ያለው ፣ለፖለቲካ ፍጆታ የማይውል ንፁህ መሰረተ ልማት ወሳኝ መሆኑን ፓርቲው በፅኑእንደሚያምን ገልፆ ዛሬ እንደ አዲስ ኢህአዴግ ያነሰው በአባይ ወንዝ ላይ ግድብ መስራትና ማልማት አስፈላጊነት ለዘመናት ሲነሳ የነበረ ጉዳይ እንደሆነም አስታውሷል፡፡ የአባይን ጉዳይ በተመለከተ ከአንድ አመት የተመረጡት የግብፅ ፕሬዝዳንት መሀመድ ሙርሲ ሃሳባቸው ተቀባይነት ይኑረውም አይኑረውም ከተቃዋሚዎች ጋር እንደተነጋገሩ የሱዳን መንግስት የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታት የተሻለ ብሄራዊ መግባባት ለመፍጠር እየጣረ እንደሆነ የገለፀው አንድነት “የኢትዮጵያ መንግስት ግን በግትርነት ማሰርና መፈረጁን በመቀጠል የሀገራዊ መግባባት አደጋ እየሆነ ነው” ብሏል በመግለጫው፡፡ በመሆኑም አንድነት አምስት ነጥብ ያለው አቋም እንዳለው አስታውቋል፡፡

የግብፅና የኢትዮጵያ መንግስት ከፀብ አጫሪ ድርጊትና ፕሮፓጋንዳ እንዲታቀቡና የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት ላይ እንዲያተኩሩ፣ አባይን መጠቀም የኢትዮጵያ የተፈጥሮ መብት እንዲሆኑ እንዲታወቅ፣ ሁለቱ ሀገራት የአባይን ጉዳይ የውስጥ ፖለቲካቸው ማብረጃ ከማድረግ እንዲቆጠቡ፣ አገራዊ መግባባት አሁኑኑ እንዲፈጠር መንግስት ሀላፊነቱን እንዲወጣና የአባይ ጉዳይ የፖለቲካ መጠቀሚያ መሆኑ እንዲያበቃ የሚሉት የፓርቲው አቋሞች ሆነው ሰፍረዋል፡፡ ከመገደቡ በፊት ማለቅ የነበረችው ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ምንድን ናቸው? ግንቦት ሀያ ደርግ የወደቀበት የህዝብ በዓል ሆኖ ሳለ ለምን የፓርቲ በዓል ትላላችሁ? ግድቡ ሲበሰር የተቃውም አቅጣጫን ለማስቀየር ነው ስትሉ ነበር አሁንም ሁለቱ አገሮች የውስጥ ችግራቸውን ማብረጃ እንዳያደርጉት እያላችሁ ነው፣ በግብፅና በኢትዮጵያ ጉዳይ ያላችሁ ቁርጥ ያለ አቋም ምንድነው? ኢትዮጵያ በታሪኳ ለህዝብ የሚያስብ መሪ አጋጥሟት አያውቅም ብላችኋል የእነ እምዬ ምኒሊክ ውለታን ዘንግታችሁት ነው የሚሉና መሠል ጥያቄዎች ከጋዜጠኞች ተነስተው ምላሽ ተሠጥቶባቸዋል፡፡

የአንድነት ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በሠጡት ምላሽ “በእኛ በኩል ሁለቱ አገሮች ወደ ከፋ ጦርነት እንዳያመሩ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንዲደረግ እንፈልጋለን” ብለዋል፡፡ የሙርሲን መንግስት ተቃዋሚዎች በሠኔ ወር መጨረሻ እናስለቅቃለን በማለታቸው ሙርሲ በአባይ ጉዳይ ነገሩን፡፡ ለማረሳሳት ጥረት ማድረጋቸው የማይቀር እንደሆነ ዶ/ር ነጋሶ ጉዳዩ በአትኩሮት ታይቶ በእኛ መንግስት በኩል እልባት ሊበጅለት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ “የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎችን አስታጥቀን ችግር እንፈጥራለን የሚሉት ግብፆች ስህተት የሚጀምረው የኢትዮጵያን ተቃዋሚዎች አለማወቃቸው ላይ ነው” ያሉት የአንድነት ምክትል ሊቀመንበር አቶ ግርማ ሰይፉ፣ በበኩላቸው ይህ አይነት አባባላቸው የግብፅ ህዝብ አስተያየት ነው ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል፡፡ “እንዲህ አይነት ውይይት በኢትዮጵያም ቢካሄድ የአባይ ወንዝ አቅጣጫ ተቀይሮ የኢትዮጵያን ምድር ያጠጣ የሚል ኢትዮጵያዊ አይጠፋም” ያሉት አቶ ግርማ፣ ይህ ሀሣብ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ይወክላል የሚል እምነት እንደሌላቸው አስታውቀዋል፡፡

ተቃዋሚን ማስታጠቅ በሚለው ሀሳብ ላይ አንድነት በአገር ጥቅምና በኢትዮጵያዊነት ላይ ፈፅሞ እንደማይደራደርና ሊታሠብም እንደማይገባ በአፅንኦት ገልፀዋል - አቶ ግርማ፡፡ “ግንቦት 20 እኔን አይወክለኝም” ያሉት አቶ አስራት ጣሴ ደርግ መውደቁ ጥሩ ነገር ሆኖ ከግንቦት ሀያ የሚጠበቁት ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፍትሆች ባልተሟላበትና መፍትሄ ባላገኙበት ሁኔታ ግንቦት ሀያ የፓርቲ በዓል እንጂ የህዝብ ሆኖ ህዝብን ሊወክል እንደማይችል ተናግሯል፡፡ አንድም ለህዝብ የሚያስብ መሪ የላትም በሚለው ጉዳይ ላይ እኔ አፄ ቴድሮስን ብንወዳቸውም የሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ የተዋጣላቸው ነበሩ ለማለት አስቸጋሪ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ “መንግስት አሁንም ቢሆን የግብፅን ጉዳይ በቸልታ ሊመለከተው አይገባም” ያሉት የአንድነት ዋና ፀሃፊ አቶ አስራት ጣሴ በዚህ ጉዳይ ላይ ተቃዋሚዎች ከዲያስፖራውና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት አገራዊ መግባባት ላይ መድረስ አለበት ብለዋል፡፡ ከግድቡ ስራ በፊት ማለቅ የነበረባቸው ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች መካከል የናይል ተፋሰስ ትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ማፅደቂያ አዋጅ መፅደቅ ከነበረበት ዘግይቶ የፀደቀበት ምክንያት አንዱ ነው ብለዋል አቶ ግርማ ሰይፉ፡፡

Published in ዜና

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አካል የሆነው የአባይ ወንዝ አቅጣጫ የማስቀየር ስራ መከናወኑንና በግብፅ በሱዳን እና በኢትዮጵያ የተቋቋመው የኤክስፐርቶች ቡድንን ሪፖርት ይፋ መደረግን ተከትሎ ከግብፅ በኩል እየተሰሙ ያሉ ጉዳዮችን በሚመለከት የመንግስታቸውን አቋም እንዲያብራሩ ከውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥያቄ የቀረበላቸው በኢትዮጵያ የግብፅ አምባሳደር እስከአሁን ማብራሪያቸውን አላቀረቡም፡፡ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሀመድ ከማል አሚር፤ በግድቡ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ለመወያያት በቀጣዮቹ ቀናት አዲስ አበባ እንደሚገቡ የተለያዩ ሚዲያዎች የዘገቡትና በኢትዮጵያም በኩል እንደሚመጡ መረጃው ያለ ቢሆንም፣ በተባለው መሠረት ይመጣሉ ተብሎ እንደማይጠበቅ ከምንጮቻችን ለመረዳት ችለናል፡፡ በሁለቱ አገሮች መካከል ስላለው ጉዳይ ሰሞኑን ማብራሪያ የሰጡት የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽነር ዲላሚኒ ዙማ፤ ኢትዮጵያና ግብፅ ችግሮቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ አሳስበዋል፡፡

ግብፅ በ1929 እና በ1959 የተፈረሙ ስምምነቶችን መሰረት በማድረግ “ታሪካዊ መብቴ ነው” በማለት ትሟገታለች፤ ሌሎቹ የተፋሰሱ አገሮች ደግሞ በ2010 የተፈራረሙትን በወንዙ ላይ የግብፅን ፈቃድ ሳይጠይቁ ለመስራት ተስማምተዋል ያሉት ኮሚሽነሯ፤ ጉዳዩ በአዲሱ ስምምነት እንጂ በቅኝ ገዢዎች ዘመን በተደረገው ስምምነት መታየት የለበትም ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል የሱዳን የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አሊ አህመድ ከርቲ፤ ሰሞኑን አዲስ አበባ በመምጣት ከጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ጋር ባደረጉት ውይይት፣ ሱዳን የኤክስፐርቶች ቡድን ያቀረበውን ሪፖርት እንደተቀበለችውም አስታውቀዋል፡፡ የነጭ አባይ ምንጭ የሆነችው የዩጋንዳ ፕሬዚደንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ በበኩላቸው፤ በግብፅ ላይ መረር ያለ ትችት ሰንዝረዋል፡፡

የግብፅ መሪዎች፤ የቀድሞው አመራሮችን የተጣመሙ ፖሊሲዎች መከተል እንደሌለባቸውና የግድቡ መሰራት ለሌሎች አገራት ስጋት ሊሆን እንደማይችል ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡ ማንኛውም አፍሪካዊ ግብፅ እንድትጎዳ አይፈልግም፤ ይሁን እንጂ ግብፅም ጥቁር አፍሪካውያንን መጉዳቷን መቀጠል የለባትም ብለዋል - ሙሴቬኒ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የሱዳኑ ፕሬዚደንት አልበሽር፤ ለሶስት ቀን የሚቆይ ጉብኝት ለማድረግ ከትናንት በስቲያ ኤርትራ የገቡ ሲሆን የፕሬዚደንት ጉዳዮች ሚኒስትር፤ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር እና የፀጥታ እና የደህንነት ሚኒስትሮቻቸው አብረው መጓዛቸውንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ፀሃፊ ባንኪሙን የሁለቱን ሀገሮች መሪዎች በቀጣዮቹ ሁለት ቀናት በስልክ እንደሚያነጋግሩ ይጠበቃል፡፡

Published in ዜና

በሽብርተኝነት ወንጀል ክስ ቀርቦበት የ18 ዓመት እስራት የተፈረደበት እና ቃሊቲ ማረሚያ ቤት የሚገኘው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፤ ከባለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ማንኛውም ሠው እንዲጠይቀው መደረጉን ባለቤቱ ጋዜጠኛ ሠርካለም ፋሲል ለአዲስ አድማስ ገለፀች፡፡ ላለፉት 22 ወራት ከአራት ሰዎች በስተቀር ማንም እንዳይጠይቀው ተከልክሎ እንደነበር የገለፀችው ሰርካለም፤ “አሁን ተመስገን ነው ልዩ ጠባቂም የተከለለ ቦታም ሳይዘጋጅ ረጅም ሠዓት ማዋራትና መጠየቅ ችያለሁ” ስትል ደስታዋን ገልፃለች፡፡

ከ10 ቀናት በፊት ሀሙስ ማለዳ ልትጠይቀው ስትሄድ በግምት 40 ሠዎች ብቻ በሚኖሩበት ዞን ሶስት እንደተለመደው ለ10 ደቂቃ አይታው መመለሷን የገለፀችው ሰርካለም፣ ቅዳሜ ዕለት ለ30 ደቂቃ የተፈቀደውን የመጠየቂያ ሰዓት ጠብቃ 4፡30 ስትደርስ “እስክንድር እዚህ የለም” ሲሏንመባሏንና ድንጋጤ ላይ መውደቋን ፣ በኋላ ከ170 በላይ የተለያዩ እስረኞች ወዳሉበት ዞን ሁለት መዛወሩን ሠምታ በመሄድ ያለ ልዩ ጠባቂ በነፃነት ለረጅም ሠዓት አዋርታው መመለሷንና፣ ይህን የሠሙ አንዳንድ ወዳጅ ዘመዶች መጠየቅ መጀመራቸውን በደስታ ገልፃለች፡፡

“ከዚህ በፊት እኔ፣ እናቴ፣ አክስቱና የአክስቱ ባል ነበርን የምንጠይቀው፣ ልንጠይቀው ስንሄድም አምስተኛው ሰው ፖሊስ ነው፤ አብሮን ተቀምጦ የምናወራውን ይሠማል፣ለብቻው የተከለለ ቦታም ነበር ስናስጠራው የሚመጣው” ያለችው የእስክንድር ባለቤት፣ “እንዴት እንደሆነ ባላወቅነው ሁኔታ አሁን እንደማንኛውም እስረኛ በነፃነት እየጠየቅነው ነው፡፡ በዚህም ደስተኛ ሆኛለሁ” ስትል ተናግራለች፡፡ ምንም እንኳ በአሁኑ ሠዓት በነፃነት መጠየቅ ብንጀምርም ጉዳዩ ወደፊት ቀጣይነት ይኑረው አይኑረው እርግጠኛ ሆኖ መናገር እንደማይቻል ጋዜጠኛ ሠርካለም ለአዲስ አድማስ ጨምራ ገልፃለች፡

Published in ዜና

አዲሱን የቤቶች ምዝገባን ተከትሎ የነባር ቤቶች ተመዝጋቢዎች ስማችን ኮምፒተር ውስጥ እንደሌለና፣ በእኛ ቁጥር የሌሎች ስም ተመዝግቦ እንደሚገኝ ተነግሮናል በማለት ቅሬታቸውን ለአዲስ አድማስ ገለፁ፡፡ ወ/ሮ መሠረት ጐሌ በ1997 ዓ.ም በቤት ፈላጊነት ሲመዘገቡ በተሰጣቸው ቢጫ ካርድ ላይ ስማቸውና የምዝገባ ቁጥራቸው በትክክል መስፈሩን ይናገራሉ፡፡ እስካሁን ግን ቤት ስላልደረሳቸው አዲሱን የቤቶች ምዝገባ እድል ለመጠቀም በነባር ተመዝጋቢዎች ዘርፍ ለመመዝገብ ሲጠይቁ፣ ስማቸው ኮምፒውተር ውስጥ አለመኖሩ እንደተነገራቸው ይገልፃሉ፡፡ በተሰጣቸው ቁጥርም የእሳቸው ስም ሳይሆን የሌላ ግለሰብ ስም ተመዝግቦ እንደሚገኝና ግለሰቡም ቤቱን መረከባቸውን ወ/ሮ መሠረት ይናገራሉ፡፡

ምናልባት ቁጥሩ ተሳስቶ ይሆናል በሚል በስማቸው ቢፈለግም የእሳቸውን ምዝገባ የሚጠቁም መረጃ አለመገኘቱን የተናገሩት ቅሬታ አቅራቢዋ፤ “ይሄ በጣም ተንኮል ያለበት አሠራር ነው፤ ያልተመዘገበ ሰው ቤት ወሰደ ሲባል አላምንም ነበር” በማለት አቤቱታቸውን ለበላይ ሃላፊ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል፡፡ ሌላው ቅሬታ አቅራቢ አቶ ታምራት ከበደ እንዲሁ በራሳቸውና በመጀመሪያ ልጃቸው ስም በቤት ፈላጊነት ተመዝግበው እንደነበርና በእነሱ የምዝገባ ቁጥር ሌሎች ሰዎች ቤት መውሰዳቸውን ገልፀዋል፡፡ “በወቅቱ መዝጋቢዎቹ ካርዱን ከጣላችሁ ቤቱን አታገኙም፤ ቁጥራችሁን ያዙ እያሉ ስለነገሩን ቁጥሩን በማስታወሻ ደብተር በመፃፍ ይዤው ነበር” የሚሉት አቶ ታምራት፤ አሁን ግን ከእነአካቴው ስማችን እንደሌለ ተነግሮናል ብለዋል፡፡

በእሳቸው እና በልጃቸው ስም ምትክም የሁለት ሌሎች ግለሰቦች ስም መገኘቱንና ሁለቱም ቤቱን መረከባቸውን ተናግረዋል፡፡ “እንዴት በእኛ ምዝገባ ቁጥር የሌሎች ግለሰቦች ስም ተመዘገበ?” ሲሉ የሚጠይቁት አቶ ታምራት፤ ነገሩ ሆን ተብሎ የተፈፀመ ሊሆን እንደሚችል ጥርጣሬያቸውን ገልፀዋል፡፡ ቅሬታቸውን ለማቅረብ ቤቶች ልማት አስተዳደር ኤጀንሲ የሄዱ ነባር ተመዝጋቢዎች፣ ቅሬታቸውን በየወረዳና ክ/ከተማ ጽ/ቤት እንዲያቀርቡ ተነግሮናል ብለዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የኤጀንሲው ሥራ አስኪያጅ አቶ መስፍን መንግስቱ፤ በ1997 ዓ.ም በተደረገው የቤት ፈላጊዎች ምዝገባ የቁጥሮች መተራመስ መፈጠሩንና ቁጥሮቹ እንደ አዲስ (ከ01-453ሺ ድረስ) መስተካከላቸውን ጠቁመው፤ በዚህም ምክንያት የተመዝጋቢዎቹ የምዝገባ ቁጥርና ስማቸው ተለያይቷል ብለዋል፡፡ ዋጋ ያለው የያዙት ካርድ ሳይሆን ስማቸው በኮምፒውተር ላይ መኖሩ ነው ያሉት አቶ መስፍን፤ ከተመዘገቡ ስማቸው የማይኖርበት ምክንያት የለም ይላሉ፡፡ እንዲህ አይነት ቅሬታዎች በተደጋጋሚ እንደቀረበላቸው በመግለጽም ትክክለኛ ማስረጃ ያላቸውን አጣርተን በነባር ምዝገባ እንዲካተቱ እናደርጋለን ብለዋል፡፡ ማስረጃ ሳይኖራቸው ቅሬታ የሚያቀርቡ ግለሰቦች ግን ጊዜው ሳያልፍባቸው እንደ አዲስ እንዲመዘገቡ አሳስበዋል - ሥራ አስኪያጁ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የ10/90 እና የ20/80 ተመዝጋቢዎች ቁጥር 200ሺህ እንደደረሰ ለማወቅ ችለናል፡፡

Published in ዜና

የአዳማ ከተማ ነዋሪ የሆኑት የ90 ዓመትና የ83 ዓመት የዕድሜ ባለፀጐቹ የፍቅርም ባለፀጐች ናቸው - ለ70 ዓመት በትዳር ዘልቀዋል፡፡ አቶ አሰፋ አበበ እና ወ/ሮ በየነች ታፈሰ በነገው ዕለትም 70ኛ ዓመት የፕላቲኒየም ኢዮቤልዩ የጋብቻ በዓላቸውን በአዳማ ያከብራሉ፡፡ ወ/ሮ በየነች ከአቶ አሰፋ ጋር በጋብቻ ሲጣመሩ የ13 ዓመት ታዳጊ እንደነበሩ የጠቆሙት በአዲስ አበበባ ዩኒቨርስቲ የቴክኖሎጂ ተቋም ተባባሪ ፕሮፌሰር ረሆኑትና የጥንዶቹ የበኩር ልጅ ኢንጂነር አበባየሁ አሰፋ፤ ወላጆቻቸው 14 ልጆችን ለማፍራትና 26 የልጅ ልጆችን ለማየት እንደበቁ ገልጿል፡፡ ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው በከፍተኛ የትምህርት ማዕረግ ተመርቀው በአገር ውስጥና በውጪ አገራት በግልና በመንግስት የስራ ሃላፊነት ላይ እንደሚገኙም ኢንጂነሩ ይናገራሉ፡፡ 70 ዓመት በዘለቀው የጋብቻ ህይወታቸው ጥንዶቹ አንዴም ሳይለያዩ በፍቅርና በመከባበር መኖራቸውን የበኩር ልጃቸው መስክረዋል፡፡

Published in ዜና

“ግንባታው ህገ-ወጥ በመሆኑ ሊፈርስ ችሏል” የወረዳ 11 ፍ/ፅ/ቤት

                    በቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 11 ውስጥ ጥቁር ድንጋይ ለማምረት የ7 ሚሊዮን ብር ኢንቨስትመንት ፈቃድ አውጥተው በስራ ላይ የሚገኙት የደረጀ በለጠ የጥቁር ድንጋይና ገረጋንቲ ማምረቻ ድርጅት ባለቤት አቶ ደረጀ በለጠ ለድርጅታቸው እቃ ማከማቻ ፈቃድ ወስደው የገነቡት የሁለት ሚሊዮን ብር መጋዘን ያለአግባብ ፈርሶብኛል ሲሉ አማረሩ፡፡ የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ፍትህ ጽ/ቤት በበኩሉ፤ ግንባታው ህገወጥ በመሆኑ ሊፈርስ ችሏል በማለት ምላሽ ሰጥቷል፡፡ በዓመት እስከ 1 ሚሊዮን ብር ግብር ከፋይ እንደሆኑ የተናገሩት የድርጅቱ ባለቤት፤ በ70ሺህ ካሬ ሜትር ይዞታቸው ላይ ለሚያካሂዱት የጥቁር ድንጋይ ማምረት ሥራ ከስራው ጋር ተያያዥነት ያለውና እስከ ድርጅቱ የስራ ዘመን ማብቂያ የሚቆይ ጊዜያዊ ግንባታ አካሂደው እንዲጠቀሙ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን በ29/06/2004 ዓ.ም የሰጣቸውን የፈቃድ ደብዳቤ አቶ ደረጀ በዋቢነት አቅርበዋል፡፡

ድርጅታቸው ከ80 በላይ ሠራተኞችን ቀጥሮ እንደሚያስተዳድር የተናገሩት ባለሀብቱ፤ አንድም ከህግ ውጭ እንዳልተንቀሳቀሱ ገልፀው፣ አፍርስ ሲባሉ ወደ ህግ በማምራት ከፍ/ቤት የእግድ ትዕዛዝ ማውጣታቸውን ተናግረው፣ ከእግዱ በኋላ በፍ/ቤት ከወረዳው ጋር ክርክር መያዛቸውን ገልፀዋል፡፡ “በክርክሩ ወቅት ሚያዚያ 10 ቀን 2005 ፍ/ቤት ቀርበን ለውሳኔ ግንቦት 21 ተቀጠርን” ያሉት አቶ ደረጀ፤ የፍ/ቤቱ ቀጠሮ ከመድረሱ አንድ ወር በፊት (ሚያዚያ 21 ቀን) ከሳሽና ተከሳሽ በሌሉበት ፍ/ቤቱ እግዱን አንስቷል፣ እንዲፈርስም አዟል በሚል ለውሳኔ በተቀጠረበት ግንቦት 21 ቀን መጥተው መጋዘኑን እና በውስጡ ያለውን ንብረት ያለማስጠንቀቂያ በግሬደር እንዳፈረሱባቸው በምሬት ገልፀዋል፡፡ በቦታው ተገኝተን ለመታዘብ እንደቻልነው መጋዘኑ ከነተሰራበት አይጋ ቆርቆሮ፣ ብሎኬትና ብረታ ብረት ፈርሷል፡፡ “ይግባኝ እንኳን እንዳልጠይቅ እኔ በማላውቀው መንገድ ፍ/ቤቱ ውሳኔ ሰጥቶ አንድ ወር ሙሉ የውሳኔ ቀጠሮውን እየጠበቅሁ እንድቆይ አድርጐኛል፡፡ በዚህም ሞራሌ ተነክቶና በዜግነቴ ላይ ጥርጣሬ አድሮብኛል” ብለዋል አቶ ደረጀ፡፡

የአቶ ደረጀ ጠበቃ አቶ ደሶ ጨመደ በበኩላቸው፤ ፍ/ቤቱ ግንቦት 21 ቀን ለውሳኔ ቀጠሮ ተሰጥቶ አጀንዳቸው ላይ መመዝገባቸውን ገልፀው፣ ፋይሉን ከቀጠሮው ወር በፊት ማን እንዳንቀሳቀሰው ሳናውቅ ሚያዚያ 21 ቀን ውሳኔ መስጠቱ ግራ አጋብቶናል” ብለዋል፡፡ በቦሌ ክ/ከተማ የወረዳ 11 ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት ወ/ሮ ኤልሳቤት መንግስቱ፤ ባለሀብቱ በስራ ላይ እንዳሉ፣ በገነቡት መጋዘን ክርክር ላይ እንደነበሩ እና በፍ/ቤት እግድ ማውጣታቸውን እንደሚያውቁ ተናግረው፣ የፍርድ ሂደቱ በወረዳው ፍ/ጽ/ቤት የሚካሄድ በመሆኑ መረጃ እንደሌላቸው ገልፀውልናል፡፡ “መጋዘኑን አውቀዋለሁ የፈረሰው ህገ-ወጥ ነው ተብሎ ነው” ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚዋ፤ በ2004 ዓ.ም ወረዳው ህገወጥ የሆኑ ግንባታዎችን ማፍረሱንና የአቶ ደረጀ መጋዘንም ከዚሁ ጋር በተያያዘ እንዲፈርስ ታዞ እንደነበር ገልፀዋል፡፡ በወረዳው የፍትህ ጽ/ቤት ሃላፊ የሆኑት ወይዘሪት አንቀፀ ዮሐንስ በበኩላቸው፤ አቶ ደረጀ ከአካባቢ ጥበቃ ባስልጣን የጥቁር ድንጋይ ማምረት ፈቃድ አውጥተው እንደሚንቀሳቀሱ ገልፀው፤ ወረዳ 11 ውስጥ ያለው ቦታ ሙሉ በሙሉ ሰነድ አልባ መሆኑንና ማንኛውም ግለሰብ ግንባታ ሲያካሂድ ወረዳው የግንባታ ፈቃድ መስጠት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ አቶ ደረጀ ከወረዳው ፈቃድ ሳይወስዱ በመገንባታቸው መጋዘኑ ሊፈርስ እንደቻለም ሃላፊዋ ገልፀዋል፡፡

ከአካባቢ ጥበቃ ቀጥታ ለወረዳ 11 የተፃፈውን የፈቃድ ደብዳቤ አስመልክተን ላነሳነው ጥያቄ ሃላፊዋ ሲመልሱ፤ አካባቢ ጥበቃ ፈቃድ ሲሰጥ መነሻው ወረዳው ሊሆን እንደሚገባ የገለፁት ወ/ሪት አንቀፀ፤ አካባቢ ጥበቃ የፈቃድ ደብዳቤ ቢጽፍላቸውም የገነቡት ግን የወረዳውን ይሁንታ ሳያገኙ በመሆኑ፣ በፍ/ቤት ክርክሩም ሚያዚያ 21 ቀን ፍ/ቤቱ እግዱ እንዲነሳና መጋዘኑ እንዲፈርስ በመወሰኑ ሊፈርስ እንደቻለ አስረድተዋል፡፡ ለግንቦት 21 የውሳኔ ቀጠሮ ተይዞ እንዴት በአንድ ወር ቀድሞ ውሳኔ እንዳገኘ ተጠይቀው፤ ይሄ የቦሌ ክ/ከተማ ፍትህ ቢሮ ነገረፈጆችን እንጂ እኔን አይመለከትም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የቦሌ ክ/ከተማ ፍትህ ቢሮ የፍ/ቤቱን ነገረ ፈጅ ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ ግን አልተሳካም፡፡

Published in ዜና

ጋናውያን ከሊቅ እስከ ደቂቅ “የእኛ መሪ ክዋሜ ንክሩማህ፤ ተራ መሪ ሳይሆን “ኦሳጊይፎ” (ድል አድራጊ) እና የመላ አፍሪካ ተምሳሌት ወደምትሆን ነፃና የበለፀገች ጋና የሚወስደን መሲህ መሪ ነው” ብለው በከፍተኛ አድናቆትና ፍቅር እልል ብለውላቸዋል፡፡ እሳቸውም “አዎ! እኔ ተራ መሪ ሳልሆን ለተለየ ተልዕኮ የመጣሁ ልዩ መሪ ነኝ” ብለው በአደባባይ አረጋግጠውላቸዋል፡፡ ይህ የፕሬዚዳንት ንክሩማህ የአደባባይ ላይ ንግግር እንዲሁ በንግግር ብቻ ቀርቶ ቢሆን ኖሮ ለእርሳቸውም ሆነ ለጋናውያን መልካም ነገር በሆነ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ይህ አስተሳሰባቸው፣ በፖለቲካና በኢኮኖሚ አመራራቸው እጅግ የተዋጣላቸውና የተሳካላቸው መሪ እንደሆኑ በእርግጠኝነት እንዲያምኑ አደረጋቸው፡፡ በዚህ የተነሳም ይበልጡኑ ብቸኛና እንኳን ሰው ጥላቸውንም የማያምኑ ክፉኛ ተጠራጣሪ እንዲሆኑ በማድረጉ፣ ከእለት ወደ እለት ከህዝቡ እየራቁ መሄድ ጀመሩ፡፡

በ1957 ዓ.ም ጋና ነፃነቷን የተቀዳጀችበትን ቀን አስመልክቶ በተካሄደው ታላቅ የራት ግብዣ ላይ ከተዋወቁ በኋላ፣ የአንድ ሰሞን አንሶላ ተጋፋፊ ወዳጃቸው የነበረችው ደቡብ አፍሪካዊቷ ቆንጆ ጀኖቪቫ ማሪያስ በፃፈችው የህይወት ትዝታ መጽሐፏ፤ “ንክሩማህ በፖለቲካ ረገድ እየተሳካለት በሄደ ቁጥር፣ የቅርብ ወዳጆቹንና የስራ ባልደረቦቹን የፈለገውን ያህል ለእሱ ታማኞች ቢሆኑም እንኳ ይበልጥ እየጠራጠራቸውና እያራቃቸው መሄድ ጀመረ፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜም በራሱ ብቸኝነት ውስጥ እየሰጠመና ከአብዛኛው ህዝብ ራሱን እያገለለ መሄድ ጀመረ፡፡ ከህዝቡ ይልቅም ሊሰማው ይፈልጋል ብለው የሚገምቱትንና ከፍተኛ የበላይነት ስሜቱን የሚያጠናክርለትን ነገር ብቻ እየመረጡ የሚነግሩትን የፓርቲ ካድሬዎችን ድጋፍ ብቻ ማግኘት ቻለ፡፡” በማለት ፅፋለች፡፡

ፕሬዚዳንት ንክሩማህ፤ በዚህ የብቸኝነት አለማቸው ውስጥ እየኖሩም ቢሆን ታዲያ ከፍተኛ የሆነ የስልጣን ግንብ መገንባት ችለዋል፡፡ ጋና ሪፐብሊካዊ ሀገር እንደሆነች የሚደነግገውና በ1960 ዓ.ም የፀደቀው አዲሱ የአገሪቱ ህገመንግስት፤ ለፕሬዚዳንት ንክሩማህ በፈለጉ ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ እንዲመሩ፤ ፓርላማው የሚያወጣቸውን ህጐችና ውሳኔዎች እንዲሽሩና ማንኛውንም የመንግስት ባለስልጣን በፈለጉበት ጊዜ ማባረር እንዲችሉ ከፍተኛ ስልጣን አጐናጽፎአቸዋል፡፡ ፓርላማው ጨርሶ የማይቆጣጠረውና ኦዲት የማይደረግ የፕሬዚዳንቱ የመጠባበቂያ ፈንድም አቋቁመዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ንክሩማህ በዚህ ብቻ ሳይወሰኑም፣ የሀገሪቱን የመገናኛ ብዙሀን ማለትም ራዲዮ፣ ቴሌቪዥንና ጋዜጦች ሙሉ በሙሉ በቁጥጥራቸው ስር ማድረግ ቻሉ። በሊቀመንበርነት የሚመሩትን የህዝብ ጉባኤ ፓርቲ በመጠቀምም፣ ከፍተኛና መሠረተ ሰፊ የቁጥጥር መረብ በመዘርጋት ስልጣናቸውን በብቸኝነት አጠናከሩ፡፡

የህዝብ ጉባኤ ፓርቲ፤ ግንባር ቀደምና የበላይ ገዥ ፓርቲ መሆኑን በማወጅ፣ ጠቅላላ የጋና የመንግስት መስሪያ ቤቶች፤ የሰራተኛ፣ የገበሬና የወጣት ማህበራት ሁሉ በፓርቲው ስር እንዲሆኑ አደረጉ፡፡ ከፓርቲው ቢሮዎች ጀምሮ እንደጋና ሴቶች ካውንስል፣ የግንባር ቀደም ታጋዮች ድርጅት፣ የጋና የሰራተኛ ብርጌዶች፣ የጋና ወጣት ታጋዮች ማህበር ወዘተ እስካሉት የሲቪልና የፖለቲካ ድርጅቶች ድረስ የንክሩማሂዝም ርዕዮተ አለምንና የንክሩማህን መመሪያዎችና ትዕዛዞች በመላው የጋና ምድርና ህብረተሰብ ዘንድ ሌት ተቀን እንዲያስፋፉ ትዕዛዝና ሃላፊነት ሰጧቸው፡፡ “የነብርን ጅራት አይዙም፤ ከያዙም አይለቁም።” የሚለው እድሜ የጠገበ የአፍሪካውያን አባባል አፍሪካውያን መሪዎች ለራሳቸው በሚመቻቸው መልኩ “የስልጣንን ጅራት አይዙም፤ ከያዙም አይለቁም” በሚል ቀይረውታል፡፡ በአፍሪካ ሀምሳ የነፃነት አመታት ውስጥ በተደጋጋሚ እንደታዘብነው፣ ለአብዛኞቹ የአፍሪካ መሪዎች ስልጣን ማለት የነብር ጅራት ማለት ነው።

አስቀድመው የሚይዙት፡፡ ከያዙት ግን ጨርሰው የማይለቁት፡፡ በዚህ የተነሳም ለእነዚህ መሪዎች የተቃዋሚዎቻቸውና ተቀናቃኞቻቸው ህልውና ማለት የነብሩ ጥርስና ጥፍሮች ማለት ናቸው። እናም በማናቸውም አይነት ዘዴ ቢሆን መወገድ አለባቸው፡፡ ለእነዚህ መሪዎች፣ ተቃዋሚቻቸውንና ተቀናቃኞቻቸውን ቸል ማለት ወይም ንቆ መተው፣ ካምሱሩ ከተፈታ ቦንብ ላይ ሃሳብን ጥሎ ተደላድሎ እንደመቀመጥ ማለት ነው፡፡ ከሞላ ጐደል በሁሉም የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ የሚገኙ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች፤ ስልጣን በያዙት መሪዎች የሚገደሉት፣ የሚታሰሩትና ከፍተኛ መንፈሳዊና አካላዊ እንግልት የሚቀበሉበት ዋነኛ ምክንያትም ይሄው ነው፡፡ የጋናና የአፍሪካ ነፃነት መሲሁ መሪ ክዋሜ ንክሩማህም ከእነዚህ የተለዩ መሪ አልነበሩም፡፡ ይህን ሁሉ ስልጣን ይዘውና መፈናፈኛ የሌለው ከፍተኛ የቁጥጥር መረብ ዘርግተውም ቢሆን የስልጣን የቁጥጥርና የበላይነት ጥማታቸው ቅም ሊለው አልቻለም፡፡ በተለይ ደግሞ ተቃዋሚዎቻቸው በነፃነት ሲዘዋወሩ ማየት ጨርሰው ሊቋቋሙት የሚችሉት ነገር አልነበረም፡፡ ለፕሬዚዳንት ንክሩማህ የተቃዋሚዎቻቸው ህልውና እንደአይናቸው ብሌን የሚሳሱለትን ስልጣናቸውን መገዳደር ብቻ ሳይሆን እኩያ የሌለውን የበላይነት ስሜታቸውን መንካትና የመሲህነት ክብራቸውን ዝቅ ማድረግ ማለት ነበር፡፡ እናም ፕሬዚዳንት ንክሩማህ፤ ለዚህ ዝግጁ የሆነ ልብም ሆነ ትዕግስት ፈጽሞ አልነበራቸውም፡፡

ይሁን እንጂ በዶክትሬት ዲግሪ ደረጃ የተማሩት ትምህርትና ልባቸውን አለቅጥ ጢም አድርጐ የሞላው የታላቅነት መንፈሳቸው፤ የጊኒው ፕሬዚዳንት አህመድ ሴኩቱሬ፣ የማላዊው ፕሬዚዳንት ካሙዙ ባንዳና ሌሎች በወቅቱ የነበሩ የአፍሪካ ፕሬዚዳንቶች ተቀናቃኞቻቸውንና ተቃዋሚዎቻቸውን ለማስወገድ እንዳደረጉት አይነት በጠራራ ፀሐይና በአደባባይ በጥይት ግንባራቸውን እየቀነደቡ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ በጄ አላላቸውም፡፡ ፕሬዚዳንት ንክሩማህ ይህንን ከማድረግ ይልቅ ተቃዋሚዎቻቸውን የማስወገድ ቀጣዩን እርምጃቸውን ዘመናዊና ህጋዊ መሠረት ለማስያዝና ሽፋን ለመስጠት በመወሰን ከ1958 ዓ.ም የቅድሚያ መከላከል እስር ህግን አወጁ፡፡ ይህ አዋጅ መንግስት የፈለገውን ማንኛውንም ጋናዊ ያለአንዳች የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ለማሰርና ያለአንዳች ፍርድ እስከ አምስት አመት ድረስ አስሮ የማቆየት ስልጣን አጐናጽፎታል፡፡ ፕሬዚዳንት ንክሩማህም ይህንን አዋጅ በመጠቀም አንዳች አይነት የህግም ሆነ የፖለቲካ አቧራ ሳያስነሱ የልባቸውን መስራት ችለዋል፡፡ ንክሩማህ፣ ይህንን አዋጅ ለፓርላማው አቅርበው ሲያፀድቁ አስራ ሁለት ተቃዋሚ የፓርላማ አባላት ቀድሞ ነገር አዋጁ ለማንና ለምን እንደተረቀቀ ስለማያውቁ፣ ፓርላማው ውድቅ እንዲያደርገው ተማጽነውም ተቃውመውም ነበር፡፡

አዋጁ ከፀደቀ በኋላ የማታ ማታ የፈሩት አልቀረላቸውም፡፡ አዋጁ በፀደቀበት አመት በቁጥጥር ስር ውለው ወህኒ ከተወረወሩት ሰላሳ ስምንት ተቃዋሚዎች ውስጥ አስራ አንዱ እነዚሁ ተቃዋሚ የፓርላማ አባላት ነበሩ፡፡ ፕሬዚዳንት ንክሩማህ፤ ፓርላማውን ተቃዋሚ አልባ ለማድረግ የነበራቸውን እቅድ በዚህ አይነት ካሳኩ በኋላ ፊታቸውን ወደ ሌሎች ተቃዋሚዎቻቸው ላይ አዞሩ፡፡ ይህንን አዋጅ በመጠቀምም፣ በ1961 ዓ.ም ሶስት መቶ አስራ አንድ፣ በ1963 ዓ.ም አምስት መቶ ሰማኒያ ስድስት፣ በ1965 ዓ.ም ደግሞ አንድ ሺ ሁለት መቶ የሚሆኑ ተቃዋሚዎቻቸውን ከያሉበት አሳፍሰው ወህኒ በመወርወር፣ አንዳንዶቹ በደህንነት ሀይል በደረሰባቸው ከፍተኛ አካላዊ ጉዳትና በእስር ቤቱ ኢ-ሰብአዊ አያያዝ የተነሳ ህይወታቸውን እንዲያጡ አስደርገዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ ለንደን በስደትና በትምህርት ሳሉ ጀምሮ የቅርብ ጓደኛና የፀረ ኮሎኒያሊዝም የትግል አጋራቸው የነበሩትና በደረሰባቸው ኢሰብአዊ እንግልትና የህክምና እጦት በእስር ቤት እንዳሉ በ1965 ዓ.ም ህይወታቸው ያለፈው ዶክተር ዳንቃህ ይገኙበታል፡፡ በ1964 ዓ.ም ፕሬዚዳንት ንክሩማህ፤ ጋናን ከብዙሀን ፓርቲ ስርአት አራማጅ አገርነት ወደ ባለ አንድ ፓርቲ አገርነት ለመቀየር በግላቸው ወሰኑና ህዝበ ውሳኔ እንዲዘጋጅ ቀን ቆርጠው ትዕዛዝ ሰጡ፡፡ ህዝበ ውሳኔው ከመካሄዱ በፊት ታዲያ እሳቸው በዋናነነት የሚቆጣጠሩት የመንግስት ብዙሀን መገናኛዎች፣ በህዝብ ውሳኔው የማይሳተፍና የፕሬዚዳንቱን ውሳኔ በመቃወም ድምፅን የሚሰጥ ከበድ ያለ ቅጣት እንደሚቀጣ ማስፈራራታቸውን አጧጧፉት፡፡ ለምሳሌ “ጋናያን ታይምስ” የተባለው መንግስታዊ ጋዜጣ ህዝቡን ያስፈራራው “የሚስጥር ድምጽ አሰጣጥ የሚባለውን አሠራር መከታ በማድረግ ልታታልሉን የምትፈልጉ ሰዎች ሁሉ በደንብ ማወቅ ያለባችሁ ትልቅ ቁምነገር፣ እኛን ማታለል የምትችሉበት ጊዜ ያከተመ መሆኑን ነው፡፡” በማለት ነበር፡፡ ጋናን ወደ አንድ ፓርቲ አገርነት የመቀየሩ ውሳኔ እሳቸውን በምድረ ጋና ያሉ ብቸኛው የፓርቲ መሪ ከማድረግ ውጪ ተቃዋሚ ፓርቲዎችንና ፖለቲከኞችን ከጨዋታ ውጪ በማድረግ ረገድ ለንክሩማህ የፈየደላቸው ነገር አልነበረም፡፡

ምነው ቢባል ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች ፕሬዚደንቱ ቀደም ብለው በወሰዷቸው የአፈናና የማስወገድ እርምጃዎች ጨርሰው ከጋና የፖለቲካ ጨዋታ ውጭ ሆነው ነበርና። ፕሬዚደንት ንክሩማህ፤ በ1965 ዓ.ም በተካሄደው ብሔራዊ ምርጫ ስማቸውን በክፉ እያነሱ በሀሜት ሲቦጭቋቸው ተገኝተዋል ተብለው በቢሮአቸው የቀረቡላቸውን ሁለት ጋናውያን ፍላግ ስታፍ ህንፃ እየተባለ በሚጠራው ፕሬዚደንታዊ ፅህፈት ቤት ግቢ ባቋቋሙት የዱር አራዊት መጠበቂያ ፓርክ ውስጥ እንዲገቡ በማስገደድ፣ በአንበሳ ተበልተው እንዲሞቱ አስደርገዋል እየተባሉ በቅርብ የስራ ባልደረቦቻቸው ሲታሙ ኖረዋል፡፡ ፕሬዚደንት ንክሩማህ ይህን ፓርክ ያቋቋሙት ወዳጆቻቸው የሆኑ የአፍሪካና የሌሎች ሀገራት መሪዎች በስጦታ ባበረከቱላቸው የዱር አራዊቶች ነበር፡፡ ለምሳሌ ሰዎቹን የበላውን አንበሳ ያበረከቱላቸው አባባ ጃንሆይ ሲሆኑ ጉማሬውን የሰጧቸው ደግሞ የላይቤርያው ፕሬዚደንት ቶልበርት ተብማን ነበሩ፡፡ በፓርኩ ውስጥ የሚገኘውን ምን የሚያህል ዘንዶ ያበረከቱላቸው ደግሞ የኩባው ፕሬዚደንት ጓድ ፊደል ካስትሮ ነበሩ፡፡ ጋናን በብቸኝነት የመምራት ኃላፊነት የተሸከመው የህዝብ ጉባኤ ፓርቲ፣ በሊቀመንበሩ በንክሩማህ ፈላጭ ቆራጭ አመራር ስር በመውደቁ ብዙም ሳይቆይ ለመበስበስና ለሙስና አደጋ በእጅጉ ተጋለጠ፡፡ የፓርቲው አባላት የሆኑ ሚኒስትሮችና የፓርላማ አባላት መደበኛ ስራቸው የራሳቸውን፣ የቤተሰባቸውን፣ የጐሳና የብሔር አባሎቻቸውን ጥቅም ማሳደድና ከፍተኛ የግል ሀብት ማከማቸት ብቻ ሆነ፡፡ ሚኒስትሮች ከእያንዳንዱ የመንግሥት ፕሮጀክት አስር በመቶ ሲቦጭቁ፣ ሌሎች የበታች ሹሞች ደግሞ እንደየደረጃቸው የመንግሥትን ሀብት መቀራመት ስራዬ ብለው ያዙት፡፡ በሙስናና የግል ሀብት በማካበት በኩል የማይታሙት ፕሬዚደንት ንክሩማህ፤ ጉዳዩ በጣም ሲያሳስባቸው በ1961 ዓ.ም ሙስናን ለመዋጋት ቃል በመግባት፣ በሙስና የተዘፈቁ የመንግሥትና የፓርቲ ባለስልጣኖችን አጥብቀው አወገዙ፡፡

የተወሰኑ ባለስልጣኖቻቸውንም ከስራ አባረሩ፡፡ የሙስናን ጉዳይ የሚያጣራና የባለስልጣኖቻቸውን ሀብት፣ ቤት፣ መኪናና ውሽሞቻቸውን ሁሉ የሚመረምር ልዩ ኮሚቴ አቋቋሙ፡፡ ይሁን እንጂ የተቋቋመው ኮሚቴ ስለአከናወነው ተግባር አንዲትም ነገር ትንፍሽ ሳይልና ይኑር ይፍረስ ሳይታወቅ ደብዛው ጠፍቶ ቀረ፡፡ ፕሬዚደንት ንክሩማህ፤ ጋናን ወደ ዘመናዊ የኢንዱስትሪ አገርነት ለመለወጥ ያወጡትን እቅድ በተግባር ለመለወጥ ያደረጉት ጥረት በመጀመሪያው ሁለትና ሦስት አመታት ደህና ይመስል ነበር፡፡ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎችና መንገዶች በብዛት መገንባት ችለዋል፡፡ ለተጠቃሚው በርካሽ ዋጋ የኤሌክትሪክ ሃይል ማቅረብ ያስቻለውና በቮልታ ወንዝ ላይ የተገነባው የሀይድሮ ኤሌክትሪክ ጣቢያ የተጠናቀቀውም በዚህ ጊዜ ነበር፡፡ ታላላቅ የልማት ውጤቶችን በፍጥነት ለማየት ትእግስት ያጡት ፕሬዚደንት ንክሩማህ፤ ቁጥር ስፍር የሌላቸውን ታላላቅ ፕሮጀክቶች ባጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቁ በአናት በአናቱ ማዘዝ ጀመሩ፡፡ በዚህ ጊዜ ነገሮች ሁለ ካቅሟ በላይ የሆኑባት ጋና፣ በኢኮኖሚ ውጥረት ውስጥ ወደቀች፡፡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በ1961 ዓ.ም የአለም የኮካዋ ምርት ገበያ ዋጋ በመውደቁ፣ መንግሥት በሀገሪቱ ላይ ከፍተኛ ታክስና ግብር እንዲጥል አስገደደው፡፡ ይህም በበኩሉ ከፍተኛ የሆነ የፍጆታ ሸቀጦች ዋጋ መናርንና ሊቋቋሙት ያልተቻለ ከፍተኛ የኑሮ ውድነትን አስከተለ፡፡ ይህንን በመቃወምም የወደብና የባቡር ሠራተኞች የስራ ማቆም አድማ መቱ፡፡ የአድማው ዜና የተነገራቸው ፕሬዚደንት ንክሩማህ፤ እንዴት ተደፈርኩ ብለው በንዴት ጧ ፍርጥ አሉ፡፡ የጦፈው ንዴታቸው ወደ እርሱ እንዳይዞር የፈራው የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትራቸው፣ በጋና ብሔራዊ ሬዲዮ የቀጥታ ስርጭት በመግባት፣ የስራ ማቆም አድማውን የመቱት የወደብና የባቡር ሠራተኞች “አሳፋሪ አይጦች ናቸው” በማለት በስድብ አጥረገረጋቸው፡፡ ፕሬዚደንት ንክሩማህ ግን እንደሚኒስትሩ አልተሳደቡም፣ የደህንነትና ልዩ የፖሊስ ኮማንዶዎቻቸውን በመላክ አድማውን ሰጥ አደረጉት፡፡

ተመሳሳይ አድማና አመፅ እንዳይነሳም ይግባኝ የማይባልበት ፍርድ የሚሰጥ ልዩ ፍርድ ቤት በማቋቋም ዳኞችንም ራሳቸው መርጠው ሾሙ፡፡ ይህ እርምጃ ተመሳሳይ የስራ ማቆም አድማ እንዳይከሰት በሚገባ ረድቷቸዋል፡፡ በከፍተኛ ፍጥነት ወደ አስቸጋሪ የኢኮኖሚ ማጥ ውስጥ ለመግባት እየተንሸራተተች የነበረችውን ጋናን ለመታደግ ግን ምንም አይነት አቅም አልነበረውም፡፡ ፕሬዚደንት ንክሩማህ፤ በመላው አፍሪካ ብቸኛው አንፀባራቂ ኮከብ መሪ ለመሆን የወጠኑት ውጥን በእግሩ ቆሞ መሄድ እንዳቃተው በግልፅ ታየ፡፡ የተባበሩት የአፍሪካ መንግሥትን በማቋቋም፣ በፕሬዚደንትነት ለመምራት የነደፉትን እቅድ፣ ተግባራዊ ለማድረግ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሽንጣቸውን ገትረው ቢወተውቱም እህ ብሎ የሚያዳምጣቸው የአፍሪካ መሪ ማግኘት ሳይችሉ ቀሩ፡፡ ህልምና እቅዳቸው እንደጉም በኖ በመጥፋቱ ስሜታቸው ክፉኛ የተጐዳው ፕሬዚደንት ንክሩማህ፤ ከበርካታ የአፍሪካ መሪዎች ጋር በተለይ ደግሞ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ከሆኑ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ጋር የፊት ለፊት ግጭት ውስጥ ገቡ፡፡ የእነዚህን ሀገራት መሪዎች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ “የፈረንሳይ የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ አሻንጉሊቶች” እያሉ መዝለፍና በነገር መወረፍ ስራዬ ብለው ተያያዙት፡፡ ከሁሉም ሀገራት ይልቅ ግን ፕሬዚዳንት ንክሩማህ ጐረቤቶቻቸው ከሆኑት ከቶጐ፣ ከኮትዲቭዋር፣ ከናይጄሪያ፣ ከቡርኪናፋሶና ከኒጀር ጋር አይንና ናጫ ሆኑ፡፡ ንክሩማህ ከእነዚህ ሀገራት ጋር የጀመሩት በነገር መናቆር ብቻውን አላጠገባቸውም፡፡

እናም የእነዚህን ሀገራት መሪዎች ከስልጣን በማስወገድ በሌላ አሻንጉሊት መሪ ለመተካት በመወሰን፣ ተቃዋሚ ቡድኖችን ማደራጀት፣ ማሰልጠንና ማስታጠቅ ጀመሩ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ስልጡን ነፍሰ ገዳዮችን በማሰማራት መሪዎችን ለማስገደል የተለያዩ ሙከራዎችን ማድረግ ቀጠሉ፡፡ የቶጐውን ፕሬዚደንት ሲልቫነስ ኦሊምፒዬን ለማስገደል ያደረጉት ሙከራ ከሽፎ፣ ሙከራውን ያደረጉት የጋና የደህንንት ኮማንዶዎች ማንነት እንደታወቀ፣ ሰባት የአፍሪካ ሀገራት ፕሬዚደንት ንክሩማህን በማውገዝ፣ ከጋና ጋር ያላቸውን የዲፕሎማሲ ግንኙነት ወዲያውኑ አቋረጡ፡፡ የአገራቱ እርምጃ ግን ፕሬዚደንት ንክሩማህን በሰው ጉዳይ ጣልቃ ከመግባትና ከጠብ አጫሪነት ድርጊታቸው ሊገታቸው አልቻለም፡፡ በፕሬዚዳንት ንክሩማህ ቀጥተኛ ትዕዛዝ የሚንቀሳቀሰው የጋና የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ፣ በቻይናና በምስራቅ ጀርመን ባለሙያዎች የሚታገዝ በርካታ የፀረ መንግስት ሽምቅ ተዋጊዎች ማሰልጠኛ ጣቢያዎችን በማቋቋም፣ በዘጠኝ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ፀረ መንግስት እንቅስቃሴዎችን ይመራ ነበር፡፡ በ1965 ዓ.ም በእነዚህ ካምፖች የሰለጠነ አንድ አፍሪካዊ፣ የኒጀር ፕሬዚዳንት የነበሩትን ሃማኒ ዲዬሪን ለመግደል ያደረገው ሙከራ ከሽፎ በቁጥጥር ስር እንደዋለ፣ ፕሬዚዳንት ንክሩማህ ለደረሰባቸው መሰጠነ ሰፊ ውግዘትና ወቀሳ ኮሚክ የሆነ መልስ ሰጥተዋል፡፡ “የተባበሩት የአፍሪካ መንግስት ተቋቁሞ ቢሆን እኮ እንዲህ ያለ የግድያ ሙከራ አይካሄድም ነበር!” በ1962 ዓ.ም ነሐሴ ወር ላይ ግን ፕሬዚደንት ንክሩማህ፣ ፈጽሞ ያልገመቱት ነገር ደረሰባቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን “በሰፈሩት ቁና መሠፈር አይቀርም” እያሉ እንደሚተርቱት፣ በራሳቸው ላይ የግድያ ሙከራ ተደረገባቸው፡፡ ወዲያውኑም የህዝብ ጉባኤ ፓርቲ ዋና ፀሐፊ የነበሩትን ታዊያ አዳማፊዬና ሁለት ሚኒስትሮቻቸውን ለግድያ ሙከራው ዋና ተጠያቂ በማድረግ፣ ፍርድ ቤት አቀረቧቸው፡፡ የከፍተኛው ፍርድ ቤት ዳኛ ግን ወንጀሉን ለመፈፀማቸው በቂ ማስረጃ አላገኘሁም በማለት ተከሳሾቹን በነፃ አሰናበቷቸው፡፡

በዚህ እጅግ የተበሳጩት ፕሬዚዳንት ንክሩማህ፤ ዳኛውን በማባረር በአንድ ጀንበር ውስጥ ለመንግስቱ አደጋ ነው ያሉትን የከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔ የመሻር መብት የሚያጐናጽፋቸውን ህግ አስረቅቀው በፓርላማ ማስፀደቅ ቻሉ፡፡ ከዚያም ራሳቸው በመረጧቸው ዳኞች፣ በከፍተኛው ፍርድ ቤት አዲስ ችሎት አስችለው፣ ተከሳሾቹን በሞት ፍርድ እንዲቀጡ አስደረጉ፡፡ ከወራት በኋላ ግን ምህረት አድርጌላቸዋለሁ በማለት፣ የሞት ቅጣቱን በእድሜልክ እስራት ቀየሩላቸው፡፡ ይህ ከሆነ ከሁለት አመት በኋላ፣ በ1964 ዓ.ም እንደገና ሁለተኛው የግድያ ሙከራ በአንድ የጋና ፖሊስ ኮንስታብል አማካኝነት ተሞከረባቸው። እንግሊዝ ሀገር በሚገኘው በዝነኛው የሳንድኸርስት ወታደራዊ አካዳሚ በሰለጠኑ መኮንኖች ይመራ የነበረው የጋና የጦር ሃይል፣ በወቅቱ ከነበሩት ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የጦር ሃይል በተሻለ ሁኔታ ጠንካራ ዲሲፕሊን የነበረውና በእለት ተዕለት የመንግስት እንቅስቃሴ ውስጥ እጁን የማያስገባ የጦር ሃይል ነበር። የተንኮታኮተው የጋና ኢኮኖሚ የፈጠረው ከፍተኛ የኑሮ ውድነት፣ የጦር ሀይሉን እንደተቀረው የጋና ህዝብ በቁንጥጫው ቢመዘልገውም ቃሉን ጠብቆ መዝለቅ ችሏል፡፡ በ1965 ዓ.ም አጋማሽ ላይ ግን ፕሬዚዳንት ንክሩማህ በህይወት ዘመናቸው ሙሉ ሠርተውት የማያውቁትን ትልቅና እጅግ አደገኛ ስህተት ፈፀሙ። የጋናን መንግስታዊና የሲቪል ተቋማት እንዳሉ በፓርቲው ቁጥጥር ስር ለማድረግ የጀመሩትን እንቅስቃሴ በጦር ሃይሉ ላይም ለመፈፀም በማሰብ፣ የጦር ሀይሉን ዋና ዋና ተቋማት በፓርቲው ካድሬዎች ለማስያዝና የፓርቲውን ሰላዮችም በጦር ሀይሉ ውስጥ አስርገው ለማስገባት ተንቀሳቀሱ፡፡

ይህን ጊዜ ለወትሮው ድምፁ ተሰምቶ የማያውቀው የጋና ጦር ሃይል ከዳር እስከዳር በመንቀሳቀስ፣ ፕሬዚዳንቱ ከዚህ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ በፀባይ አሳሰበ፡፡ ፕሬዚዳንት ንክሩማህ ግን የጦር ሀይሉ ማሳሰቢያ የተለሳለሰ በመሆኑ ይመስላል ንቀው አጣጣሉት፡፡ የጦር ሀይሉ ከበፊቱ ያልተለየ ማሳሰቢያ ለሁለተኛ ጊዜ ሰጠ፡፡ በዚህ ጊዜም ፕሬዚዳንት ንክሩህማ፤ የጦር ሀይሉን ማሳሰቢያ መናቅና ማጣጣል ብቻ ሳይሆን “ለመሆኑ ለእኔ ማሳሰቢያ የምትሠጡኝ እናንተ ማን ሆናችሁ ነው!” ብለው በጦር ሀይሉ መሪዎች ላይ በቁጣ ቱግ አሉ፡፡ የፕሬዚዳንቱ ሀይለኛ ቁጣ ያረፈበት የጋና ጦር ሃይል፣ በዚህ ጊዜ ፕሬዚዳንቱን “እባክዎ አደብ ይግዙልን” የሚል ማሳሰቢያውን ለሶስተኛ ጊዜ ለማውጣት አልፈለገም፡፡ የደረሰበትን ቁጣ ዋጥ አድርጐ ብቻ ፀጥ አለ፡፡ ይህ ከሆነ አራት ቀን በኋላ ግን ሶስት ጀነራሎች በጋና ጦር ሀይሎች ዋና ኤታማጆር ጽሕፈት ቤት ውስጥ ከረፋዱ እስከ ተሲያት የደረሰ ረጅም ስብሰባ አካሂደው ተለያዩ፡፡

ከሶስቱ ጀነራሎች አንዱ “የቤተመንግስት ቅልብ ጦር” እየተባለ የሚጠራው የፕሬዚዳንቱ የክብር ዘበኛ ሬጂመንት አዛዥ የነበሩት ጀነራል ኢግናቲየስ አቺምፓንግ ነበሩ፡፡ የካቲት 24 ቀን 1966 ዓ.ም ፕሬዚዳንት ንክሩማህ፤ የቬየትናም ጦርነትን እሸመግላለሁ ብለው ወደ ቬየትናም ዋና ከተማ ሃኖይ ለመሄድ፣ በጠዋቱ አውሮፕላን ተሳፍረው ቻይና ቤይጂንግ ከተማ ገቡ። ከፕሬዚዳንቱ ቤተመንግስት ጋር አንድ ትልቅ አጥር ተጋርቶ በተሰራው ባለ አንድ ፎቅ ህንፃ ውስጥ ባለው ቢሮአቸው ውስጥ ከወዲያ ወዲህ ሲንጐራደዱ የነበሩት ጀነራል ኢግናቲየስ አቺምፓንግ ይህን እንዳረጋገጡ፣ ከማን እንደሆነ ያልታወቀ አንድ የስልክ ጥሪ ደረሳቸው፡፡ ስልኩን አነጋግረው ከዘጉት በኋላ፣ ከጠረጴዛቸው መሳቢያ ኡዚ ጠመንጃቸውን ይዘው ከቢሮአቸው ወጡ፡፡ ከአንድ ሰአት በኋላም የጋና ሬዲዮና ቴሌቪዥን፣ ፕሬዚዳንት ክዋሜ ንክሩማህ ከስልጣን እንደተባረሩና አዲሱ መሪ ጀነራል ኢግናቲየስ አቺምፓንግ መሆናቸውን አወጀ፡፡ በአክራና በኩማሲ ከተሞች ህዝቡ በነቂስ ግልብጥ ብሎ በመውጣት “ንክሩማህ መሲሁ መሪያችን አይደለህም!” እያለ በደስታ ጨፈረ፡፡ እስከ 1971 ዓ.ም ድረስ በጊኒ በጥገኝነት የኖሩት ንክሩማህም ሚያዚያ 27 ቀን 1972 ዓ.ም ቡካሬስት ውስጥ በህክምና ላይ እንዳሉ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ
Page 10 of 17