በራፕ የሙዚቃ ስልት የሰው ጆሮ ውስጥ ለመግባት የቻለው ዊል ስሚዝ፤ አሁን በሚታወቅበት የፊልም አለም የሰው አይን ውስጥ የገባው በአጋጣሚ አይደለም። በአገራችን እንደተለመደው፤ “የጥበብ አድባር ጠርታኝ…” ምናምን ብሎ ነገር የለም - በሆሊውድ። ዊል ስሚዝ፣ አይቶና አስቦ፣ አስልቶና ቀምሮ ነው ወደ ሆሊውድ መንደር የዘለቀው። “በተመልካች ብዛትና በትፋማነት፣ በተወዳጅነትና በኦስካር ሽልማት ሪከርድ የሰበሩ ፊልሞች ምን አይነት ናቸው?” የሚል ጥያቄ ነው የዊል ስሚዝ መነሻ። የብዙ አመት መረጃዎች ተሰበሰቡ። ከአንድ እስከ አስር የወጡት ፊልሞች፣ አንድ በአንድ ተመረመሩ። ከአስሩ መካከል ሰባቱ፣ “የሳይንስ ፊክሽን ፊልሞች ናቸው። ከእነዚህም መካከልም በርካታዎቹ ፊልሞች ውስጥ፣ ልዩ ፍጡራን ወይም የሌላ አለም “ሰዎች” ይታያሉ።

በተወዳጅነትና በትርፋማነት ብቻ ሳይሆን፣ ብዙ የኦስካር ሽልማት በማግኘትም፣ የሳይንስ ፊክሽን ፊልሞች ቀዳሚ መሆናቸውን የተመለከተው ዊል ስሚዝ፣ ለኤጀንቱ የሰጠው “መመሪያ” አጭርና ግልፅ ነበር - “የሳይንስ ፊክሽን ፊልም ውስጥ መስራት ይኖርብናል” የሚል። ልክ ያጣ ድፍረት ይመስላል። ምክንያቱም፣ ዊል ስሚዝ በወቅቱ፣ በአንድ የቴሌቪዥን ድራማ ላይ ቢሰራም፣ በሆሊውድ ፊልም ላይ አንድም ጊዜ ሳይሳተፍ ነው፣ ፊልም አማርጦ ለመስራት የፈለገው። ግን እንዳሰበው ተሳካለት። ‘ባድ ቦይስ’ ከተሰኘው አክሽን ፊልም በመቀጠል፣ ዊል ስሚዝ በሰፊው ለመታወቅ የበቃው ‘ኢንዲፐንደንስ ዴይ’ በተሰኘው የሳይንስ ፊክሺን ፊልም ላይ ነው። ከሌላ አለም የመጡ ፍጡራን የሰው ዘርን ለማጥፋትና አለምን ለማውደም ዘመቻ ሲያካሂዱ በሚታዩበት በዚሁ ፊልም አለምን ከጥፋት፣ የሰው ልጅን ከእልቂት የሚታደጋቸው ዊል ስሚዝ ነው። ከዚያም ‘ሜን ኢን ብላክ’ በተሰኙ ሶስት ፊልሞች ላይ፣ ከሌላ አለም የሚመጡ ልዩ ፍጡራንን እየተጋፈጠ ምድርንና የሰው ዘርን ከጥፋት ሲያድን ይታያል።

በዚህም አላበቃም፤ ‘አይ ሮቦት’ ፊልም ላይ እንደገና አለምን ከክፉ ሮቦቶች ያድናታል። ‘አይ አም ሌጀንድ’ በተሰኘው ፊልም፤ የሰው ዘር በክፉ የበሽታ ወረርሽን ጨርሶ እንዳይጠፋ የሚያደርገው ዊል ስሚዝ ነው። ‘ሃንኩክ’ ፊልም ላይም፣ የሰው ልጅን ከጥፋት ይታደጋል። የዊል ስሚዝ ሚስት ጃዳ በበኩሏ፣ በሁለት የ‘ማትሪክስ’ ፊልሞች የድርሻዋን ትወጣለች። የ14 አመቱ ልጃቸው ጃደን ደግሞ፣ በሶስት ፊልሞች የአባትና የእናቱን መንገድ ተከትሎ እየሰራ ነው። ትንሿ ልጃቸው ዊሎው እስካሁን በአንድ ፊልም ላይ ሰርታለች። ለመሆኑ ዊል ስሚዝ እስካሁን በሰራቸው ፊልሞች የስንት ሰው ህይወት አድኗል? ታዋቂው ዋየርድ መጽሔት ሰሞኑን እንደዘገበው ከሆነ፣ ዊል ስሚዝ ከነቤተሰቡ፣ እስካሁን ከ63 ቢሊዮን በላይ ሰዎችን ከእልቂጥ አድኗል ብሏል።

ከአለም የህዝብ ቁጥር በዘጠኝ እጥፍ የሚበልጡ ሰዎች፣ በዊል ስሚዝ ቤተሰቦች ጀግንነት ከእልቂት ተርፈዋል - በፊልም ውስጥ። በእውነተኛው አለም ደግሞ፣ ዊል ስሚዝና ቤተሰቦቹ የተሳተፉባቸው ፊልሞች፣ 6 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ገቢ እንዳስገኙ ዋየርድ ገልጿል። ዊል ስሚዝና የ14 አመት ልጁ ጃደን የሰሩበት አዲሱ “አፍተር ኧርዝ” የተሰኘው ፊልም ላይ ግን፣ አለማችን ኦና ሆናለች። የሰው ዘር የላትም - የሰው ዘርን በሚያጠፉ አውሬዎች ተሞልታለች። ዊል ስሚዝና ጃደን፣ በዚህ ፊልም ሌሎች ሰዎችን ሳይሆን የራሳቸውን ሕይወት ከሞት ለማዳን ይታገላሉ።

Published in ዜና

በ “ፍትህ” ጋዜጣ “የሁለተኛ ዜግነት ህይወት እስከመቼ”፣ “የፈራ ይመለስ” እና “መጅሊሱና ሲኖዲሱ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ማጥመቂያ” በሚሉ ርዕሶች በተለያዩ እትሞች ባሰፈረው ዘገባ ተከስሶ ጉዳዩ ሲታይ የነበረው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ምስክሮችን ለመስማት ለሃምሌ ሁለት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ፡፡ ከትላንትና በስቲያ በከፍተኛው ፍ/ቤት 16ኛ ወንጀል ችሎት የጋዜጠኛው ምስክሮች ሊደመጡ ቀጠሮ የተያዘ ቢሆንም ፍ/ቤቱ የተከሳሽን የመከላከያ ቃል ሲያዳምጥና ስለምስክሮቹ ከጠበቆች መግለጫ ሲሰማ ሰዓት ያለቀ በመሆኑ የምስክሮችን ቃል ለመስማት ሌላ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ “የህዝብን ሃሳብ በማናወጥ” ፣ “ህዝብን በህገ መንግስቱ ላይ ማነሳሳትና” “የመንግስትን ስም ማጥፋት” በሚሉ ሶስት ጉዳዮች ክስ ተመስርቶበት ጉዳዩ ሲታይ የነበረው ጋዜጠኛ ተመስገን፤ የመከላከያ ምስክሮቹ ምስክርነታቸውን ለመስጠት ሀሙስ ዕለት በፍርድ ቤቱ ተገኝተው ነበር፡፡ ሆኖም በጊዜ እጥረት ሳይመሰክሩ ቀርተዋል፡፡

ከጋዜጠኛ ተመስገን ምስክሮች ውስጥ 1ኛ ምስክር ዶ/ር ያሬድ የህግ ባለሙያ ሲሆኑ ሁለተኛ ምስክር ፕ/ር መስፍን ወ/ማሪያም እና 3ኛ ምስክር ጋዜጠኛ እንዳልካቸው ሀ/ሚካኤል ከህግ፣ ከጋዜጠኝነትና ከመናገር ነፃነት እና መሰል ጉዳዮች አንፃር ምስክርነታቸውን በቀጣዩ ቀጠሮ እንደሚያቀርቡ ተገልጿል፡፡ የፌደራል አቃቤ ህጎች በ1ኛ ምስክር ዶ/ር ያሬድና በሁለተኛ ምስክር ፕ/ር መስፍን ወ/ማሪያም ላይ እንዳይመሰክሩ ተቃውሞ ያቀረቡ ሲሆን የተቃውሞው ምክንያት ዶ/ር ያሬድ የህግ ባለሙያ ቢሆኑም ህገ መንግስቱን የመተርጎም ስልጣን እንደሌላቸው በመግለፅ ሲሆን 2ኛ ምስክር የሆኑት ፕ/ር መስፍን ደግሞ ምንም እንኳ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ ሊቀመንበር የነበሩ ቢሆንም ከ1997 ዓ.ም ወዲህ በነበራቸው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ገለልተኛ ሆነው ይመሰክራሉ የሚል እምነት እንደሌለ በመግለፅ ነበር፡፡

ፍርድ ቤቱም በኋላ 1ኛ ምስክር ህገ-መንግስቱን የመተርጎም መብት ባይኖራቸውም ተከሳሽ የተከሰሱባቸው ፅሁፎች ከህግ አንፃር እና ሃሳብን በነፃነት ከመግለፅ አኳያ አግባብ ናቸው አይደሉም ያስከስሳሉ አያስከስሱም፣ በሚለው ላይ ብቻ እስከተናገሩ ድረስ ችግር እንደሌለው ጠቁሞ፤ ፕ/ር መስፍንም የኢሰመጉ ሊቀመንበር በነበሩበት ጊዜ ድርጅቱ ስላወጣቸው ሪፖርቶችና ተያያዥ ነገሮች ብቻ ከተናገሩ የፖለቲካ እንቅስቃሴያቸው ከምስክርነት ያግዳቸዋል የሚል ህግ እንደሌለ በመግለፅ የተከሳሹን ምስክሮች ቃል ለመስማት ፍ/ቤቱ ለሃምሌ ሁለት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

Published in ዜና

የሞባይል አገልግሎት ተጠቃሚዎች በውጪ ሃገር የስልክ ቁጥሮች በሚደወሉ ጥሪዎች እየተጭበረበሩ ናቸው ያለው ኢትዮቴሌኮም፣ ደንበኞቹ ጥሪውን አንስተው እንዳይመልሱ አሳሰበ፡፡ መስሪያ ቤቱ ከደንበኞች የደረሰውን ጥቆማ በማጣራት ለማጭበርበር የሚደውልባቸው የውጪ ሃገር ስልክ ቁጥሮች መሆናቸውን አረጋግጫለሁ ያላቸው የሚከተሉት ናቸው -+35418441045፣ +4238773310፣ +34518441045፣ +4238773952፣ +004238773395፣ 004238773740፣ 004238773050 እንዲሁም 0025270300504፡፡

እነዚህ ቁጥሮች የተደወለለት ደንበኛ ጥሪዎቹን ካነሳና ካነጋገረ የአገልግሎቱ ሂሳብ በእሱ እንደሚታሰብ አረጋግጫለሁ ብሏል ኢትዮ ቴሌኮም፡፡ በተጨማሪም በአጭር የጽሑፍ መልዕክት “እጣ ደርሶዎታል” በማለት ነው በ0037178912368 ቁጥር የሚላክ መልእክት የተጭበረበረና ሃሰተኛ መሆኑን ደንበኞቼ ይወቅልኝ” ብሏል፡፡ ደንበኞች በ0042፣ 0025፣ 0022፣ 0023፣ 0037 እና 0043 በሚጀምሩ የውጪ ሃገር የስልክ ቁጥሮች ለሚደወሉላቸው ጥሪዎች ማንኛውም አይነት ምላሽ እንዳይሰጡ ኢትዮ ቴሌኮም አሳስቧል፡፡

Published in ዜና
Page 17 of 17