በደቡብ አፍሪካ ተካሂዶ በነበረው የ2010 የአለም ዋንጫ ወደ ደቡብ አፍሪካ መግባት የሚያስችል የ10ሺህ ሰዎችን ቪዛ ልሰጣችሁ እችላለሁ በሚል 1200 ከሚደርሱ ዜጉች ከ25-37ሺህ ብር በነፍስ ወከፍ በመቀበል አጭበርብረዋል ባላቸው የአስካሉካን ትሬዲንግ ባለቤት አቶ ግርማዬ ገ/ሚካኤል ላይ ፍርድ ቤት የ6 አመት ከ6 ወር ጽኑ እስራት እና የ8ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ባለፈው ማክሰኞ ውሳኔ አስተላለፈ፡፡

አቃቤ ህግ በተከሳሹ ላይ ካቀረባቸው ስምንት ክሶች መካከል ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ ያላቸው በሰባት ክሶች ሲሆን ከህዳር 7 እስከ ግንቦት 2002 ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ግለሰቡ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ከ25ሺህ እስከ 37ሺህ ብር ከመውሰዳቸውም በተጨማሪ የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ዜጐች እንዲጉላሉ በማድረግ እና የንግድ ፍቃዳቸው የአስመጪነትና ላኪነት ሆኖ ሳለ ባልተፈቀደላቸው የስራ መስክ ተሰማርተው ወንጀል በመፈፀም ከሀገር ለመኮብለል ሞክረዋል ሲል ክሱን አጠናክሮ አቅርቧል፡፡

አቃቤ ህግ ግለሰቡ የፈፀሙት ከባድ የማታለል ወንጀል መሆኑን በመጥቀስ 11 የሰው ምስክሮችንና 20 የሰነድ ማስረጃዎችን ለፍርድ ቤት በማቅረብ አስረድቷል፡፡ ተከሳሹ አቶ ግርማይ በበኩላቸው፤ ወንጀሉን አልፈጸምኩም ሲሉ ክደው የተከራከሩ ሲሆን በወቅቱ የደቡብ አፍሪካ ቪዛ እሰጣለሁ ያልኩት በእጄ የተገኘን መረጃ ምክንያት አድርጌ ነው ካሉ በኋላ ይህም ሆኖ ለተበዳዮቹ ሃብትና ንብረቴን ሸጬ የሚገባቸውን ካሳ ከፍያለሁ ከማለታቸውም በተጨማሪ ሰባት የመከላከያ ምስክሮችንና ሰነዶችን አቅርበው ተከራክረዋል፡፡

የግራ ቀኙን ክርክር ሲያዳምጥ የቆየው ችሎቱ፤ ጉዳዩን መርምሮ ተከሳሹን ጥፋተኛ ናቸው ያለ ሲሆን እንደ ቅጣት ማቅለያ አቅርበውት የነበረውን ለተበዳዮች ካሳ ከፍያለሁ የሚለውን የመከራከሪያ ሃሳብ እሳቸው ፈቅደውና ተፀፅተው ሳይሆን የፍትሐብሄር ክስ ተመስርቶባቸው በመረታታቸው የፈፀሙት በመሆኑ እንደቅጣት ማቅለያነት አልቀበለውም ብሏል፡፡ተ ከሳሹም በሰባት ክሶች ጥፋተኛ ተብለው በድምሩ ስድስት አመት ከስድስት ወር ፅኑ እስራት እና በስምንት ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ሲል ወስኗል፡፡

Published in ዜና

የካሣ ክፍያው በዝግ ሂሣብ ተቀምጧል

በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 በተለምዶ ሰንጋተራ ተብሎ በሚታወቀው ቦታ ለልማት ተነሺ ናችሁ ተብለን ተገቢው ካሣና ምትክ ቦታ ሳይሰጠንና በቤቱ ላይ ከመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ ጋር ያለው ውዝግብ እልባት ሳያገኝ፣ ከ40 አመት በላይ የኖርንበት ቤታችን በግብታዊነት ፈረስብን ሲሉ የቤቱ “ህጋዊ ወራሾች” ቅሬታቸውን ለአዲስ አድማስ ገለፁ፡፡ በቤት ቁጥር 520 የተመዘገበው መኖሪያ ቤት፣ በአፄ ሃይለስላሴ ዘመን ካርታ ተሰጥቶት ህጋዊነቱ የተረጋገጠና በአንድ የቤት ቁጥር ስር ተጠቃሎ ሳለ፣ ከጐኑ ያለውና የወላጅ አባታችን እህት በሞት ሲለዩ ለአባታችን በስጦታ ያበረከቱትን ቤት፣ የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ “የኔ ነው” የሚል ክርክር በማንሣቱ፣ በማስረጃዎች አስደግፈን የቤቱ ህጋዊ ወራሾች መሆናችንን ብናስረዳም፣ የክፍለ ከተማውና የወረዳው አመራሮች ማስረጃችንን ተቀብለው ለማረጋገጥና ውሳኔ ለመስጠት ፍቃደኛ አልሆኑም - ብለዋል ቅሬታ አቅራቢዎቹ፡፡

ከቤቱ ህጋዊ ወራሾች አንዱ የሆኑት አቶ ነብዩ አባተ፤ አሁን ክርክር ያስነሳው የአክስታቸው የነበረው ቤት ከአዋጅ 47/67 በፊት ለግለሰቦች ተከራይቶ የነበረ ሲሆን አዋጁ ከወጣ በኋላ ቀበሌው በጉልበት ወስዶ ለ5 ዓመት በጽ/ቤትነት ሲገለገልበት ከቆየ በኋላ፣ በ1973 ዓ.ም ተከራክረን እንዲመለስልን በማድረግ ግብር እየገበርንበት ስንኖርበት ነበር ብለዋል፡፡ የአባታችን እህት “ድርሻዬን ለእነሱ ሰጥቻለሁ ያሉበትን የሰነድ ማስረጃ አቅርበን ነበር ያሉት አቶ ነብዩ ፤ የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ ግን ቤቱ በአዋጅ የተወረሰ ነው፤ ስለዚህ ለኛ ይገባናል የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው ተናግረዋል፡፡ ይህን መነሻ በማድረግም ክፍለ ከተማውና ወረዳው “እኛ በቤቱ ጉዳይ ላይ ያሉንን ማስረጃዎች ተቀብለው ሳይመረምሩ ክርክራችሁን ከቦታው ለቃችሁ ጨርሱ” የሚል ምላሽ በመስጠት በግብታዊነት ቤቱን ወደማፍረሱ እንደተሸጋገሩ አቶ ነብዩ ገልፀዋል፡፡

የክፍለከተማው አመራሮች ይህን ውሳኔ ያሳለፉት ለማረፊያ የሚሆን ቤትና የካሣ ክፍያ ሳይከፍሉን ነው ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ይህን መብታቸውን ሲጠይቁም፤ የካሣ ክፍያችሁ በዝግ አካውንት ተቀምጧል የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸውና ጊዜያዊ መኖሪያ ቤት ተብሎ የተሰጣቸውን ለመረከብ ወደተባለው ቦታ ሲሄዱ፣ወረዳው የተባለውን ቤት ለመስጠት ፍቃደኛ ሳይሆን መቅረቱን ገልፀዋል፡፡ “ተገቢውን አስተዳደራዊ ፍትህ አጥተናል” የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ በአሁን ሰአት በአፍራሽ ግብረ ሃይል ጣራው በፈረሰው ቤት ላይ የፕላስቲክ ክዳን ወጥረው ለመኖር እንደተገደዱና ቀጣይ እጣ ፈንታቸውም ምን እንደሆነ ማወቅ እንዳልቻሉ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የልደታ ክ/ከተማ የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ለምለም ገ/ሚካኤል፤ ቦታው ለልማት ተፈልጐ የከተማው አስተዳደር ተገቢው ካሣና ምትክ ቦታ ተሰጥቷቸው እንዲነሱ ከአንድ አመት በፊት መወሰኑን ጠቁመው ፣ በዚህ ውሣኔም በአካባቢው ያሉ ቤቶች በሙሉ ሲነሱ ይህም ቤት ከቦታው እንዲነሳ ቢወሰንም በቤቱ ላይ ከሁለቱ ወገኖች ቅሬታ በመቅረቡ መዘግየቱን አስታውቀው፣ ከዚህ በላይ መታገሱ ለሚፈለገው ልማት እንቅፋት የሚፈጥር በመሆኑ በቤቱ ውስጥ ያሉት ግለሰቦች ጊዜያዊ ቤት ተሰጥቷቸውና በዝግ ሂሣብ የካሣ ክፍያው ተቀምጦላቸው፣ ቤቱ እንዲፈርስ የመጨረሻ ውሣኔ መተላለፉን ገልፀዋል፡፡

የካሣ ክፍያውን በዝግ ሂሣብ ማስቀመጥ ያስፈለገውም በፍርድ ቤት አፈፃፀም የተወሰነለት አካል እንዲወስድ መሆኑን ሃላፊው ተናግረዋል፡፡ “የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲም ክርክር ያስነሳው ቤት የራሱ መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ አቅርቦልናል” የሚሉት አቶ ለምለም፤ ቅሬታ አቅራቢዎቹ የኛ ነው የሚሉ ከሆነ አለን የሚሉትን ማስረጃ ይዘው በፍርድ ቤት ተከራክረው ማስወሰን ይችላሉ፤ እስከዚያ ግን ቤቱ የተመደበው ካሣ በዝግ ሂሣብ ይቀመጣል፤ ጊዜያዊ የቀበሌ ቤትም ውሰዱ ብለናቸዋል፤ ለመውሰድ ግን ፍቃደኛ አይደሉም ብለዋል፡፡ “እስካሁን ድረስ ችለናል፤ መንግስት ወዳዘጋጀላቸው የቀበሌ ቤት ይግቡ፤ እኛ ግን ከዚህ በኋላ አንታገስም፤ በፍጥነት እርምጃ እንወስዳለን” ብለዋል - አቶ ለምለም፡፡

Published in ዜና

የአሽከርካሪዎችን ግንዛቤ በማዳበር በሕይወትና በንብረት ላይ እየደረሰ ያለውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ የሚያግዝ የአሽከርካሪዎች ማስተማሪያ “ሶፍት ዌር” ተዘጋጀ፡፡ ሶፍትዌሩን ከስማቸው ኮምፒዩተር ሰርቪስ ጋር በመሆን ያሰናዱት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዋና ሳጅን አሰፋ መዝገቡ እና አቶ ንፁህ ካሳ ናቸው፡፡ በትራንስፖርት ባለስልጣን ጥናት በአገሪቱ ከሚከሰቱ የትራፊክ አደጋዎች 76 በመቶ የሚሆኑት በአሽከርካሪ ስህተት የሚፈጠሩ መሆኑን የጠቀሱት አዘጋጆቹ፤ ለአሽከርካሪዎች ተገቢ የሆነ ሥልጠና በመስጠትና ሃላፊነት የሚሰማቸው አሽከርካሪዎች እንዲኖሩ በማድረግ እየደረሰ ያለውን አደጋ መቀነስና መግታት እንደሚቻል ገፀልዋል፡፡

ከአንድ ዓመት በላይ ዝግጅት የተደረገበት “ሶፍትዌር”፤ በሥዕላዊ መግለጫ የተደገፈ የመንገድ ሥነ ሥርዓትና ምልክት፣ የተሽከርካሪ የቴክኒክ ክፍሎች፣ የአሽከርካሪ ባህርይ፣ የተሽከርካሪ ቅድመ ብልሽት ጥገና እና በመሳሰሉ ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ የሚሰጥ ከመሆኑም በላይ፣ ባለሥልጣኑ ከሚሰጣቸው የመንጃ ፈቃድ ፈተናዎች ጋር የሚዛመዱ ከአንድ ሺህ በላይ የናሙና ፈተናዎችን ያካተተ ነው፡፡ ፈተናው የሚሰጠው በኮምፒዩተር እንደሆነና ከተፈታኞች መካከል 75 በመቶ የሚሆኑት ፈተናውን እንደሚወድቁ የገለፁት ዋና ሳጅን አሰፋ፤ የሶፍትዌሩ መዘጋጀት ይህንን ክፍተት ያጠበዋል ብለዋል፡፡

Published in ዜና


አድማስ አድቨርታይዚንግ እ.ኤ.አ በ1990 የተቋቋመ የግል ድርጅት ነው፡፡ አድማስ አድቨርታይዚንግ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ሁለት ዋና ክፍሎች አሉት፡፡

የህትመቱ ክንፍ አንዱ ሲሆን ሳምንታዊው ጋዜጣ አዲስ አድማስ ያሳትማል የማስታወቂያ ክንፉ ደግሞ የፊልም መስሪያስቱዲዮ እና ግራፊክ ዲዛይን ያለው ነው፡፡ ድርጅታችን በኤሌክትሮኒክስ ሆነ በህትመት ሚዲያ ላይ የሚሰራ የማስታወቂያ ኤጀንሲ ነው፡፡ የቴሌቪዢንና ሬዲዮ ማስታወቂያዎችን በመስራት በአየር ላይ ከማዋላችንም በተጨማሪ የሚዲያ ምክርና ዕቅድ አገልግሎቶች እንሰጣለን፡፡ በሚሰጠን ቅድመ መረጃ አማካይነት ማናቸውንም የቲቪ፣ሬዲዮ እና ፕሬስ ማስታወቂያዎች እንዲሁም ግራፊክ አርትስ እንሰራለን፡፡

አገልግሎታችን በሚዲያ ምርጫ ላይ ማማከር፣ማቀድ፣መከታተል፣የማስታወቂያዎቹ ያስገኙትን የመጨረሻ ውጤት መገምገምን ያካትታል፡፡ በርፉ ያልን በቂ ልምድና በቡድን የመስራት ባህል ሚዲያውን እንዴት ደንበኞቻችን በሚያረካና ውጤታማ በሚያደርግ መልኩ መጠቀም እንዳለብን እንድናውቅ አስችሎናል፡፡ አድማስ አድቨርታይዚንግ የአዲስ አበባ ንግድ ም/ቤት አባል ሲሆን በተለያዩ ባህላዊና ማሕበራዊ እንቅስቃሴዎች ንቁ ተሳታፊ ነው፡፡

Audio visual studio

የማስታወቂያ አገልግሎት እና ኦዲዮ/ቪዥዋል ስቱዲዮበላቀ የፕሮዳክሽን ደረጃው ዪታወቀው የማስታወቂያ ክፍላችን ለንግዱ ዘርፍና ለማህበራዊ ግብይት ዋነኛ አጋርነቱን አረጋግጧል፡፡ ፕሮፌሽናል የኦዲዮ/ቪዲዮ ስቲዲዮችን፡፡ በፕሮፌሽናል ዲቪ ካሜራዎች ከአማራጭ ሌልሶች ጋር የመብራትና የድምጽ መሳሪያዎች የካሜራ ክሬን በተሟላ የኤዲቲንግ ስቱዲዮ እና በሌሎች ተፈላጊ መሳሪያዎች የተደራጀ ነው፡፡ ቴክኖሎጂ ያፈራቸውን የተደራጀ ዘመናዊ መሳሪያዎች የያዘው ስቱዲዮአችን በአገራችን ካ ጥቂት ምርጥ የፊልም ስቱዲዮዎች አንዱ ያደርገዋል፡፡

አድማስ አድቨርታይዚንግ ብቁና ተፎካካሪ በሆኑ የአስተዳደር የፋይናንስ እና በጥበብ ባለሙያዎች የተሞላ ነው በድርጅቱ የሚሰሩት ተርጓሚዎች ገጣሚዎች የአርት ዳይሬክተሮች እና ጋዜጠኞች በሙያቸው የተሞከሩ የተፈተኑና በበርካታ ፕሮጀክቶች አመርቂ ውጤት ያስመዘገቡ ናቸው፡፡ በተጨማሪው ድርጅቱ በህዝቡ ዘንድ በተቀዳጀው አክብሮት እና አስተማማኝ የሥራ ሁኔታ የተነሳ በአገሪቱ የሚገኙ ምርጥ የፈጠራ ችሎታ ያላቸው ባለሙያዎች ለመቅጠርና አብረውን እንዲሰሩ ለማድረግ አስችሎታል፡፡ ለዚህም በየጊዜው ያስመዘግባቸው የስኬት ክብረወሰኖች ከቃላት በላይ ይናገራሉ፡፡

የአድማስ አድቨርታይዚንግ ኃ/የተወሰነ የግል ማህበር ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ አሰፋ በኢትዮጵያ የማስታወቂያ ኢንዱስትሪ ጉልህ ለውጥ ማምጣታቸውም ይታወቃል፡፡

በኢትዮጵያ በተፈጠረው የዲሞክራሲ ስርዓት ሚዛናዊ ሂሳዊ ጋዜጣ በመመስረት ለህብረተሰቡ የንባብና የዕውቀት ዕድል የፈጠረ ሰው ነበር፣ያሉት በቀብር ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የማስታወቂያ ሚኒስትሩ አቶ በረከት ስምኦን ሲሆኑ የሪፖርተር ጋዜጣ ባለቤትና ዋና አዘጋጅ አቶ አማረ አረጋዊ በበኩላቸው ‹‹ በኢትዮጵያ ፕሬስ የተግባር ሚና ከተጫወቱ ሰዎች ግንባር ቀደም ነው ›› ብለዋል፡፡የአቶ ድንገተኛ ሞት አስመልክተው ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ አስተያየታቸውን ሲሰጡዕ ‹‹ እንደ ህብረተሰብ ትልቅ ሰው ነው ያጣነው ›› ብለዋል፡፡

በብዙዎች ዘንድ አድንቶትን ያተረፈውንና በስምንት ድምፃውያን የተዜመውን ‹‹ ማውቀር ነው መሰልጠን ›› የተሰኘ የዘፈን ክሊፕ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት አድማስ አድቨርታይዚነግ ማሰራቱ የማታወቅ ሲሆን በቅርቡ በኮራ አሸናፊ የሆነው የድምፃዊት ፀደንያ ገ/ማርቆስ የዘፈን ክሊፕ አቶ አሰፋ እራሳአው በቅርቡ ባቋቋሙት የፊልም ስቱዲዮ መሰራቱ ታውቋል፡፡

በአድማስ አድቨርታይዚንግ ስር የሚታተመውና በአገራችን በስርጭት ብዛት ከሁለት ዓመት ወዲህ በቀዳሚነት ሥፍራ የሚገኘው የአዲስ አድማስ ጋዜጣ መስራች ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ አሰፋ ከምዕራብ አገራት የፊልም ደረጃ ጋር የሚስተካከል ፊልም ለመስራት ባላቸው ራዕይ ለየት ያለ ስቲዲዮ በመገንባት ላይ ነበሩ፡፡


Published in መረጃዎች

አቶ አሸናፊ እጅጉ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽ/ቤት ሃላፊ በመሆን ለበርካታ አመታት የሰሩ ሲሆን የፊፋ “ኮሚኒኬ” (መረጃ) ሲመጣ በመጀመሪያ የሚደርሰው ለእሳቸው ነው፡፡ ሰሞኑን የኢትዮጵያ ብሄራዊ የእግር ኳስ ቡድን ከደቡብ አፍሪካው ጋር በአዲስ አበባ ስቴዲየም ባደረገው ግጥምያ ያገኘውን ድል ተከትሎ በተሰማው አሳዛኝ ዜናና በተከሰቱ ችግሮች ዙርያ ጋዜጠኛ ሰላም ገረመው ከአቶ አሸናፊ እጅጉ ጋር ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡

አቶ አሸናፊ እጅጉ

****

“ኮሚኒኬ” ምንድነው? “ኮሚኒኬ” ማለት በጨዋታ ጊዜ ለሚከሰቱ ጥፋቶች የሚሰጡ የቢጫ እና የቀይ ካርድ ቅጣቶች የሚገልፅበት ደብዳቤ ነው፡፡ ፊፋ ኮሚኒኬን ለእኛ ይልካል፡፡ ከዚያም በፅ/ቤቱ በኩል ለቡድን መሪና ለአሰልጣኙ ይሰጣል፡፡ የሚመጣውን “ኮሚኒኬ” መነሻ በማድረግ ውይይት ታደርጋላችሁ? ውይይት አይደረግም፡፡ ደብዳቤው እንደደረሰኝ ለብሄራዊ ቡድኑ አስተላልፋለሁ፤ ለሴቶች ብሄራዊ ቡድን እና ለዋናው ቡድናችንም ደብዳቤው በአፋጣኝ እንዲደርሳቸው አደርጋለሁ፡፡ ከዚህ በኋላ ማሳረፍ የሚገባቸውን ተጫዋች የማሳረፍ ግዴታ ያለባቸውና የሚገባቸው እነሱ በመሆናቸው፣ በዚህ ጉዳይ ላይ “ማን ቢጫ አየ” ማን ቀይ አየ” ብለን የምንወያይበት ነገር የለም፡፡ ይሄ ጉዳይ መፈፀሙን የሚከታተል ሰው አለ? ማንም የለም፡፡ በአሰልጣኙ የስራ ዝርዝር ተራ ቁጥር 20 ላይ በኢንተርናሽናል ውድድር ወቅት ቀይና ቢጫ የሚያዩ ተጫዋቾችን መዝግቦ መያዝና በውሳኔው መሰረት ተግባራዊ ማድረግ የአሰልጣኙ ዋና ስራ መሆኑ ተገልጿል፡፡ አሰልጣኙም ይህን ሃላፊነት ፈርመው የወሰዱት ነገር ነው፡፡ ይህንን ማየት ይቻላል፡፡

እኔ ከቡድኑ ጋር ቦትስዋና ድረስ አልሄድኩም፡፡ ማን ይግባ የሚለውን አላውቅም፡፡ አንዳንዴ ቅጣት እያለባቸው በህመም የማይሳተፉትን ለሞራል እያሉ ይወስዷቸዋል፡፡ ስለዚህ ማንን ማሰለፍ እንዳለባቸው ማወቅ የሚገባቸውና በትዕዛዙ መሰረት መፈፀም የነበረባቸው እነሱ ናቸው፡፡ እንጂ ጉዳዩን የሚከታተል ሰው የለንም፡፡ ደብዳቤውን ስትሰጧቸው ጉዳዩን በትኩረት እንዲመለከቱ አልተናገራችሁም? እስካሁን እንዲህ አይነት አሰራር አልነበረም፡፡ ደብዳቤው ሲመጣ ተረክበን እንሰጣቸዋለን፤ ዝርዝር ጉዳዩን የሚመለከታቸው አካላት አንብበው የሚረዱ ስለሆነ፣ እንደዚህ ነው ብለን የምናስረዳበት ሁኔታ የለም፡፡ አቶ ብርሃኑ ወረቀቱን መውሰዳቸውን አምነው ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ አቶ ሰውነት አለመውሰዳቸውን ይናገራሉ፣ እዚህ ጋ ክፍተት አለ? በትክክል ክፍተት አለ፡፡

የመጣውን ኮሙኒኬ ለቡድኑ መሪ እና ለአሰልጣኙ ይሰጥ ብዬ ነው የምመራው፡፡ እዚህ ጋ ጉዳዩ ትልቅ ስለሆነ አቶ ብርሃኑ ጊዜ ስለነበረው ፈርሞ ወሰደ፡፡ መዝገብ ቤት ሰራተኛዋ አቶ ሰውነትን ጠርታ እንዲወስድ ጠየቀችው፡፡ “ቆይ ስራ አለኝ” አላት፡፡ ከዚያም ተመልሶ መጥቶ ሁለት የመዝገብ ቤት ሰራተኞች ባሉበት ወሰደ፡፡ ፀሃፊዋም በወቅቱ ወስደዋል በማለት ፈረመችበት፡፡ አልፈረሙም ነበር፡፡ አለመፈረማቸው ክፍተት ነው፤ ነገር ግን አቶ ሰውነት ማንኛውንም ደብዳቤ በሙሉ በእምነት ሳይፈርሙ ነው የሚወስዱት፡፡ ለምን ሳይፈርሙ እንደወሰዱ የጠቅኋቸው ፀሃፊዎች፤ ከዚህ ቀደምም ደብዳቤ ሳይፈርሙ እንደሚወስዱ ነገሩኝ፡፡ እኔ ግን ይሄን አላውቅም ነበር፡፡ ከደሞዝ ጭማሪ እና ከስራ ዝርዝር ደብዳቤ ውጪ ፈርመው አያውቁም፡፡ ይሄ በጣም ያሳዝናል፡፡ እንዲህ ነው ለማለት እቸገራለሁ፡፡ ስለዚህ ክፍተት አለ፡፡ የህክምና እና የቪዛን ክትትል በተመለከተ የሚመለከተው ማነው? የህክምና ሳይሆን የቪዛና የአየር ትኬት ጉዳይ ማጠናቀቅ ያለበት ጽ/ቤቱ ነው፡፡ ቀደም ሲል የክለብ ማናጀር ነበር፡፡ በአንዳንድ ምክንያቶች እንዲነሳ ተደረገ፡፡

መልሰን መቅጠር አልቻልንም፡፡ እንዲህ ሲነገር ለህዝብ ሌላ ነገር ይመስላል፡፡ ግን አንደኛ የተጫዋቾች ዝርዝር የደረሰን በጣም ዘግይቶ ነበር፡፡ በፓስፖርት አሰጣጥም ላይ ችግር ነበር፡፡ ፓስፖርት የሚያሠራ ፕሮቶኮል ሹም አለ፡፡ በአውሮፕላን ጉዞ ችግር ፓስፖርት የሌላቸው፣ ቪዛቸው የተቃጠለ፣ ሦስትና አራት ሲቀረው ነው አሰልጣኙ የሰጠን። ከጊዮርጊስም ሲመጡ ፓስፖርታቸው የሚታደስ ነበር፡፡ ያንን ለማሳደስ ኢምግሬሽን ተባብሮን በሁለት ቀን ነው የጨረሰልን፡፡ ትልቅ ባለውለታችን ናቸው። ከዚህ በኋላ ትኬት ለመቁረጥ አስመዝግበን፣ መሄጃ እንጂ መመለሻ የለም ተባልን፡፡ የእኛን ችግር እንዲያይ ለማድረግ የቡድኑን መሪ አቶ ብርሃኑን ይዘን ነበር የሄድነው፡፡ አቶ ብርሃኑ በጣም ቀናና ለማንኛውም ነገር ተባባሪያችን ነው፡፡ ይሄ ነገር ገጠመው እንጂ ጉዳዩ የአገር ጉዳይ ስለሆነ ተንሸራቶ እኛ ጋር እንዳይመጣና ችግር እንዳይፈጠር የራሳችንን ስራ ተሯሩጠን ሰርተናል፡፡ ሌላው የቢጫ ወባን ህክምና በተመለከተ ልጆቹ ካርዱን እየጣሉ እንደገና ነው የምናወጣው፡፡ እዚህም ላይ ጤና ጥበቃ ስለሚተባበረን ነው፡፡ የአገር ጉዳይ ሲባል እንደገና እናወጣለን፡፡

ስለዚህ አገርን የሚጐዳ ነገር እየሸፈንን ነው የምንሰራው፡፡ ውጤታማ ስለሆኑ ደግሞ ያስቸግራል፡፡ ሉሲዎችም ከናይጄሪያ አቻቸው ጋር ሲጫወቱ ከማሊያ ጋር በተያያዘ ችግር ተፈጥሮ ነበር ይባላል፡፡ ምን ነበር የሆነው? እኔ ማሊያ ይሰጣቸው ብዬ ስመራ፣ የናይጄሪያ ማሊያን ተቀራራቢ እንዳይለብሱ በማለት ሌላ ማሊያ እንዲሰጧቸው ገልጬ ነበር፡፡ ነገር ግን እታች ያሉት የተባለውን ሳይሆን ሌላ ማሊያ ሰጧቸው፡፡ እነሱም ማሊያውን ያዩት እዛ ከደረሱ በኋላ ነው፡፡ እንደዚህ አይነት ችግር የሚፈጥሩት ላይ ለምን እርምጃ አይወሰድም? የቡድን መሪውም ሆነ አሰልጣኙ በጥድፊያም ላይ ይሁን በምንም ማየት አለባቸው፡፡ እያንዳንዱን ነገር ተደረገ አልተደረገ ብዬ ለመከታተል አልችልም፡፡ ሲወስዱ ገልጦ መመልከት የተረካቢው ፋንታ ነው፡፡ “ካፍ” የሚል የተፃፈበትን ማሊያ ለአለም ዋንጫ ይዘው መሄድ የለባቸውም፡፡ እንደዚህ አይነት ስህተት ይታያል፡፡ እኔ እያንዳንዱን ወርጄ ጫማ ቁጥሩ ድረስ መከታተል ደረጃዬም አይደለም፡፡ ችግሩ ገፍቶ እንዳይሄድ እርምጃ አያስፈልገውም? እያንዳንዱ ሠራተኛ ሃላፊነቱን ተጠንቅቆ መወጣት ይገባዋል፡፡

ትጥቅንም የሚረከብ አካል ተጠንቅቆ መረከብ ይኖርበታል፡፡ ለምሳሌ ቦትስዋና ሲሄዱ ሁለት ማሊያ ነው የሰጠናቸው፡፡ አንዱ ማሊያ ላይ የካፍ ምልክቶች አሉ፡፡ በእጃቸው ላይ የሚለጠፉ፡፡ እነዚህ ምልክቶች አልቀውብናል፡፡ አንድ ማሊያ ላይ ብቻ ነበር የተሰራው፡፡ ችግሩ እንግዲህ ተጫዋቾቹ ማሊያዎችን አይመልሱም፡፡ ስለዚህ በየጊዜው አዳዲስ ማሊያ ነው እያሳተምን የምንሰጠው፡፡ ፊፋ የሰጠንን ደግሞ ጨረስን፡፡ ከዚህ በፊት እንደዚህ አይነት ችግር ገጥሟችሁ አያውቅም? አጋጥሞን አያውቅም፡፡ እንደዚህ አይነት ነገሮች ሲከሰቱ ጠንከር ያለ እርምጃ መውሰድ አይገባም? አሁን ችግሩ ስለተከሰተ ነው እንጂ ሁላችንም ተረባርበን ነው የሠራነው፡፡ የአገር ጉዳይ በማለት ሌት ተቀን የደከምነው ለአገራችን ውጤት እንዲመጣ ነው፡፡ የደጋፊውን ፍላጐት ለማሳካት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ችግር እንዳይከሰት የራሳችንን ውሳኔ እየሰጠን ነው በጽ/ቤት በኩል፡፡

ለምሳሌ ማንም ሰው ደብዳቤ ሳይፈርም እንዳያወጣ ወስነናል፡፡ የፊታችን ሰኞ ጠቅላላ ጉባኤ ጠርተናል፡፡ በዚህ ጉባኤ ላይ የሚያስፈልገውን ነገር መውሰድ ይቻላል፡፡ ለፌዴሬሽኑ የስራ መልቀቂያ ደብዳቤ ያስገባ አለ? እስካሁን ያስገባ የለም፡፡ ከተጠያቂነት መሸሽ አንችልም፡፡ በስራው ላይ ስህተት ተፈጽሟል፡፡ የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ ጠይቀናል፡፡ ከዚህ በኋላ ምንም ማድረግ ያለብን አይመስለኝም፡፡ ጠቅላላ ጉባኤው የሚሰጠውን ውሳኔ መጠበቅ ነው የሚሻለው።

የኮንሶ ባሕላዊ ቅርሶች በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዓለምአቀፍ ቅርስ ሆነው የተመዘገቡበትን አንደኛ ዓመት በማስመልከት የተዘጋጀ ፌስቲቫል በመጪው ሳምንት እንደሚካሄድ በደቡብ ብሔራዊ ክልል ሰገን ዞን የኮንሶ ወረዳ አስተዳደር አስታወቀ፡፡ ከሰኔ 21 እስከ 23 በካራት ከተማ የሚካሄደውን ፌስቲቫል አስመልክቶ የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ በሪቆ በላቸው ጉይታ ሲያስረዱ፣ የኮንሶን ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች ወደ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በመቀየር ከጎብኚዎች ፍሰት እንጠቀማለን ብለዋል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደው ፌስቲቫል በሲምፖዚየም፣ በጎዳና ላይ የባህልና ጥበብ ትዕይንት፣ በመሠረተ ልማት ጉብኝትና በሌሎችም ዝግጅቶች የታጀበ ሲሆን ፌስቲቫሉ በየዓመቱ የሚከበር መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በኢትዮጵያውያን የዲሞክራሲ እና የነፃነት ትግል ላይ ተንተርሶ የተፃፈው “የአሲምባ ፍቅር” መጽሐፍ ዛሬ እንደሚመረቅ ሜሮኢ መልቲሚዲያ አስታወቀ፡፡ 448 ገፅ ያለውን መጽሐፍ የደረሱት ካህሳይ አብርሃ ብስራት ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ እና ግንባር (ኢህአፓ/ኢህአሠ) ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ላይ ተመስርቶ የተፃፈው መጽሐፍ የሚመረቀው መስቀል አደባባይ በሚገኘው የቀይ ሽብር ሰማዕታት ብሔራዊ ሙዚየም ነው፡፡ “የአሲምባ ፍቅር” በ100 ብር እየተሸጠ ነው፡፡ በሌላ በኩል “ውጥንቅጥ” የተሰኘው የግጥም መጽሐፍ ነገ እንደሚመረቅ ገጣሚው አስታወቀ፡፡ ባምቢስ አካባቢ በሚገኘው ትልቁ ዮርዳኖስ ሆቴል የሚመረቀውን የግጥም መጽሐፍ የፃፈው ዮርዳኖስ ፍቃዱ ተክለማርያም ነው፡፡

Saturday, 22 June 2013 12:18

የፌዴሬሽኑ ቅሌት

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫው ማጣሪያ የሁለተኛ ዙር ግጥሚያ ጋቦሮኒ ላይ ከቦትስዋና አቻው ጋር ባደረገው ጨዋታ ሁለት ቢጫ ያየውን ምንያህል ተሾመ በማሰለፉ በፊፋ የቀረበው ክስ ለመላው የእግር ኳስ ቤተሰብ ያልተጠበቀ መርዶ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ለቀረበበት ክስ በቂ መከላከያ ማቅረብ ካልቻለ ከቦትስዋና ጋር ተጫውቶ ያስመዘገበው የ2-1 ውጤት ተሰርዞ ለቦትስዋና ቡድን በፎርፌ 3 ነጥብ እንደሚመዘገብላት ተገልጿል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያ 130ሺ ብር ቅጣት መክፈል ይጠበቅባታል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ወደ ዓለም ዋንጫ ለማለፍ መስከረም 6 ቀን 2006 ዓ.ም ከመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ የግድ ማሸነፍ ይኖርበታል፡፡ ለዚህ ሁሉ ተጠያቂው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ዝርክርክ አሰራር ነው፡፡

ከዋልያዎቹ የ2ለ1 ድል በፊት የደረሰው መርዶ መርዶው በይፋ የተሰማበት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ጋዜጣዊ መግለጫ ማክሰኞ እለት በጊዮን ሆቴል ሳባ አዳራሽ ሲሰጥ በደስታ መግለጫና በምስጋና ነበር የተጀመረው፡፡ ከዚያም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በደቡብ አፍሪካ ላይ 2ለ1 በሆነ ውጤት ካስመዘገበው ድል ጋር በተያያዘ በመላው ኢትዮጵያ በነበረው የደስታ አገላለጽ ለሞቱ ሁለት ወጣቶችም የ1 ደቂቃ የህሊና ፀሎት ተደርጓል፡፡ ሁለቱ የባህርዳር ወጣቶች የ16 ዓመት ተማሪ እና የ13 ዓመት ሊስትሮ ናቸው፡፡ ፌዴሬሽኑ በደስታ አገላለፁ የሞቱት ሁለት ወጣቶች መሆናቸውንም ቢገልጽም በመግለጫው ላይ የተገኙ አንዳንድ ጋዜጠኞች የሟቾች ቁጥር 4 ይሆናል የሞት አደጋ ያጋጠመው በባህርዳር ብቻ አልነበረም በሱልልታና በአዳማም ጭምር እንጅ ብለው እርማት አድርገዋል፡፡

ጋዜጣዊ መግለጫውን የመሩት የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ሳህሉ ገ/ወልድ፣ በደቡብ አፍሪካ ላይ በተመዘገበው የ2ለ1 ድል ዘግተናል ያልነውን ምዕራፍ እንደገና ለመክፈት ተገደናል በሚል የመግቢያ ንግግራቸው መግለጫውን የጀመሩት ፤ አስደንጋጩ መርዶ ፌዴሬሽኑ ፅህፈት ቤት የደረሰው ረቡዕ ዕለት መሆኑን በመግለፅ ነበር፡፡ ኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ በአዲስ አበባ ስታድዬም ከመገናኘታቸው ሶስት ቀናት ቀደም ብሎ ማለት ነው፡፡ ከፊፋ የመጣው የክስ “ኮምኒኬ” ረቡዕ 5 ሰዓት ላይ ለፌዴሬሽኑ በፋክስ ሲደርስ በጽ/ቤቱ ስለ እሁድ ጨዋታ አጠቃላይ ዝግጅት ለመነጋገር ተሰብስበው የነበሩት የፌዴሬሽኑ ኃላፊዎች፣ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ሳህሉ ገ/ወልድ ፤ተቀዳሚ ም/ፕሬዚዳንቱ አቶ ብርሃኑ ከበደ ፤ ዋና ፀሐፊው አሸናፊ እጅጉ ናቸው፡፡ ለፌዴሬሽኑ ኃላፊዎች አስደንጋጭ፣ የሚረብሽና ከፍተኛ የሃዘን ስሜት ውስጥ የከተተ መርዶ ሆኖባቸው እንደነበርም ገልፀዋል፡፡ ዋና ተቀዳሚ ም/ፕሬዚዳንት አቶ ተካ አስፋው፣ በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ስብሰባ ካይሮ ሄደው ነበርና ሐሙስ ሲመለሱ የፌዴሬሽኑ ኃላፊዎች አስቸኳይ ስብሰባ ተቀመጡ፡፡ እንዲህ በሚልም ተነጋገሩ፡፡ “እሁድ ጨዋታ አለን፡፡ ህዝቡ ጉጉት ላይ ነው፡፡ ተጨዋቾቹ ስሜታቸው የተነሳሳበት ወቅት ነው፡፡ ያለውን ድባብ ማፍረስ ስለሌለብን ጉዳዩን በከፍተኛ ምስጢር መያዝ አለብን” በማለት ተማማሉ፡፡ መማማሉ በየትኛውም መንገድ መረጃው እንዳይወጣ፣ የብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች እንዳይረበሹ፣ ህዝቡ ስሜቱ እንዳይጎዳ በሚል ነበር፡፡

እንደ አቶ ሳህሉ ገለፃ፣ ዋልያዎቹ የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኖ ከደቡብ አፍሪካ ጋር የተደረገውን ጨዋታ በድል በመወጣታቸው ለፌደሬሽኑ ሃላፊዎች ከእነጭራሹ ደብዝዞና ከስሞ የነበረው ተስፋቸውን አለመለመላቸው፡፡ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለዓለም ዋንጫው የመጨረሻ ማጣሪያ ምዕራፍ መግባቱን ባረጋገጠ ደስታ ተውጦ ነበር፡፡ ስለመርዶው ምንም የሚያውቀው ነገር አልነበረም፡፡ የፌዴሬሽኑ ሥ/አስፈፃሚ አባላት ሰኞ ዕለት 10 ሰዓት ላይ አስቸኳይ ስብሰባ ተቀመጡ፡፡ ስብሰባው የተፈጠረውን ሁኔታ በመገምገም እና ችግሩን ለይቶ አጠቃላይ የጋራ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ነበር፡፡ በዚህ የስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ላይ ከ11 አባላቱ ባሻገር ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻውና የጽ/ቤት ኃላፊዎች በሙሉ ተገኝተውበታል፡፡ እንደ ፌደሬሽኑ አመራሮች ማብራርያ፣ በስብሰባው የፊፋን የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ህገ ደንብ በማጣቀስ በቀረበው ክስ ዙርያ መከራከርያ ነጥቦች ተነስተው ተመክሯል፡፡

ከቀኑ 10 ሰዓት ተጀምሮ እስከ ምሽቱ 2 ሰዓት ተኩል በዘለቀው ስብሰባ፣ የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚዎች እንደየሃላፊነታቸው እና የስራ ድርሻቸው በቡድንና በተናጠል ተገማግመዋል፡፡ ስብሰባው የመደናገጥ እና የመላቀስ ድባብ እንደነበረውና ስፖርታዊ ጨዋነትን በተላበሰ መንገድ እንደተከናወነ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የተናገሩት የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ሳህሉ፣ በመገማገም መድረኩ ስህተት መፈፀሙ እንደተረጋገጠ ፤ በቀረበው ክስ ለፊፋ ይግባኝ ለመጠየቅ እና ለመከራከር እንደማይቻል ታወቀ ብለዋል፡፡ ለደረሰው ጥፋት ተጠያቂ መኖር እንዳለበት በመተማመን በየደረጃው ተጠያቂ አካላትን በመለየት በጋራ መግባባት ውሳኔ ላይ መደረሱን ሲያብራሩም ምንም አይነት ሆን ተብሎ የተደረገ (Deliberate) የተሸረበ ሴራ (sabotage) ፣ የታቀደ ተንኮል (Intentional) እንዳልሆነ ተረድተናል ብለዋል፡፡ ዋልያዎቹን ነጥብ ያስጣለው ዝርክርክ አሰራር፤ ተጠያቂዎቹ እና ቃላቸው በፌደሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ ግምገማ ላይ ለተፈፀመው ጥፋት የመጀመርያው ተጠያቂ የሆኑት ተቀዳሚ ም/ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ ከበደ ናቸው፡፡ አቶ ብርሃኑ ከበደ የቡድን መሪ ሆነው የተሾሙት የዓለም ዋንጫው የምድብ ማጣርያ በደቡብ አፍሪካ እና ኢትዮጵያ ጨዋታ ሩስተንበርግ ላይ ሲጀመር እና ከዚያም በኋላ በሁለተኛ ዙር የምድብ ማጣርያ አዲስ አበባ ላይ ኢትዮጵያ እና ሴንትራል አፍሪካ ባደረጉት ግጥሚያ የቡድን መሪ ከነበሩት አቶ አፈወርቅ አየለ ሃላፊነቱን በመረከብ ነበር፡፡ ከሁሉም በላይ በእኔ ኃላፊነት ይህ ጥፋት በመድረሱ የተሰማኝን ሃዘን መግለጽ እፈልጋለሁ በማለት ቃላቸውን መስጠት የጀመሩት አቶ ብርሃኑ ከበደ፤ በዋልያዎቹ የቡድን መሪነት ስራቸውን የጀመሩት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በጋብሮኒ ከቦትስዋና አቻው ጋር በተጋጠመበት ወቅት ነበር፡፡

የፌደሬሽኑ ፅህፈት ቤት የዚሁን ጨዋታ ኮሚኒኬ አስፈርሞ እንደሰጣቸው ቢገልፅም፤ አቶ ብርሃኑ ግን በሰጡት ቃል ፈረሙበት የተባለው ደብዳቤ ኮፒ እጃቸው ላይ እንደማይገኝ፤ እንደተሰጣቸው እንደማያስታውሱ፣ ተሰጥቷቸውም ከሆነ ደብዳቤው እንዴት ከእጃቸው እንዳመለጠ እንደማይገባቸው ነው የገለፁት፡፡ በጋብሮኒ ለተካሄደው ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ልዑካን የቪዛ ጉዳዮች እና ሌሎች ጉዳዮች የማስፈፀም ድርብ ሃላፊነት እንደነበረባቸው ያስታወሱት አቶ ብርሃኑ ከበደ፣ በወቅቱ ዋና ተቀዳሚው ም/ፕሬዚዳንት አቶ ተካ አስፋውና ዋና ፀሐፊው አቶ አሸናፊ እጅጉ ሞሪሽዬስ ውስጥ በሚደረግ የካፍ ስብሰባ ላይ ለመካፈል ሄደው ስለነበር በሎጀስቲክ ስራዎች ላይ አተኩረው እንደነበር ፣ ተቀጥረው የሚሰሩበት ከፌደሬሽኑ ውጭ ያለ ስራቸውም ለተጨማሪ ውጥረት እንደዳረጋቸው፣ በዚህ ውዥንብር ውስጥ “ደብዳቤው እንዳመለጠኝ ነው የሚገባኝ” ብለዋል፡፡ ልጆቹ ወደ ሜዳ ሲመጡ እኮ እንደ ቡድን መሪነት ብቻ ሳይሆን እንደ አሰልጣኞቹ ረዳት ሆኜ ኳሶችና የመለማመጃ ቁሳቁሶችን ይዤ ነው የምጠብቃቸው፣ ዋናው ነገር ከእጅ ላይ መጥፋቱን እንዴት ላስተውል በማለት በተሰበረ ስሜት ማብራርያቸውን የቀጠሉት አቶ ብርሃኑ፤ ከጽ/ቤት በኩልም ብርሃኑ እንደዚህ አይነት ወረቀት ሰጥተንሃል ብሎ ያስታወሳቸው እንዳልነበር በመጥቀስ፣ የልጆቹን መነሳሳት በጣም እፈልገው ስለነበር ስለሚገጥሙን ውጣ ውረዶች ለማንም ሳልናገር የጉዞ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በማስፈፀም አተኮርኩ እንጂ የቀይና ቢጫ ጉዳይ ትዝ አላለኝም ነበር በማለት አስረድተዋል፡፡ በተፈጠረው ስህተት ጥፋተኛው ራሴ እንጅ ማንም ላይ ለማላከክ አልፈልግም ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ብርሃኑ ከበደ፤ ደብዳቤው አምልጦኛል፡፡ ለምን አመለጠህ ቢባል እንኳን አላውቀውም፡፡ ከማናችንም በላይ ያዘንኩት እኔ ነኝ፡፡

ወደዚህ የመጣሁት ላገለግል ልሠራ ነው፡፡ በህይወቴ እንደዚህ አይነት ነገር እንዲያጋጥመኝ አልጠብቅም ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብን በጣም ይቅርታ እጠይቃለሁ በማለት ንግግራቸውን ቋጭተዋል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ተጠያቂ የሆኑት ደግሞ የብሄራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝን ሰውነት ቢሻውና ሌሎች አካላት ናቸው፡፡ ያጋጠመው ጥፋት ሁላችንንም ከልብ አሳዝኖናል ያሉት አሰልጣኝ ሰውነት፤ለደረሰንበት ደረጃ ሚዲያው፣ ህብረተሰቡ፣ ስራ አስፈፃሚው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሁሉም አካላት ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን ከገለፁ በኋላ በቡድን ነው እየተሰራ የነበረው ችግር ቢኖር ኖሮ ከሚዲያው በኩል ይጠቆመን ነበር ብዬ ነው አስብ የነበረው ብለዋል፡፡ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው አስተያየታቸውን ሲቀጥሉ ‹‹ከፅህፈት ቤቱ ተሰጥቶታል የተባለው ኮሚኒኬ ለአቶ ብርሃኑ ደርሶ ይሆናል፣ እኔ አልወሰድኩም፡፡ እሱ ባይደርሰው እኔ ከደረሰኝ መረጃው አለ ማለት ነው፡፡ በእንግሊዝኛ ቢፃፍም አነባለሁ፡፡ እንግሊዝኛ ማንበብ ባልችል ኖሮ ተተርጉሞ ይላክልኝ ነበር፡፡ ወረቀቱ አልደረሰኝም፡፡ ያ በመሆኑ እጅግ አዝናለሁ፡፡ ለአንዳችን ቢደርሰን ምናለበት፡፡ እኛ ወረቀቱም አንጠብቅም፡፡ ቢጫ ያዩትን ልጆች እናውቃቸዋለን፡፡ ምንያህል በደቡብ አፍሪካው ጨዋታ ያየው ቢጫ ካርድ አለ፣ ከዚያ በኋላ አፍሪካ ዋንጫ ተካሂዶ ከቦትስዋና ጋር ባደረግነው ጨዋታ ሁለተኛውን ቢጫ ካርድ አየ፡፡ ያንን የሚገልጽ ወረቀት ግን አልደረሰኝም፡፡

ከዚህ ውጭ የተቀጡ ልጆችን በሚደርሰን መረጃ መሰረት እንዳይሰለፉ እናሳርፋቸዋለን፡፡ ቢጫና ቀይ ያላቸው ተጨዋቾች ጋር እንነጋገራለን፡፡ ተጨዋቾችም ያለባቸውን ቅጣት በሜዳ ላይ ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ ጋር በማያያዝ ይነግሩናል፡፡›› በማለት አጠቃላይ ሁኔታውን ለማብራራት ሞክረዋል፡፡ ስህተቱን ሰርተን አንድ ደረጃ እንድደርስ የተፈጠረ ሁኔታ ይመስለኛል ያሉት ዋና አሰልጣኙ፤በምንሰራቸው ስራዎች ሁሉ በቂ ጥንቃቄና ትኩረት እንዲኖረን ያስተማረን ነው በማለት አሁንም ቡድናቸው የማለፍ ሰፊ ዕድል እንዳለው ለማስገንዘብ ጥረዋል፡፡ ‹‹የተሰደብንበት፣ ኢትዮጵያ የተሰደበችበት ውድድር ነው፣ በቢጫና ቀይ ጥፋት የምንተወው ነገር አይደለም፡፡ አንድ ታሪክ ሰርተን ቆመን በአደባባይ የምንናገርበት ስራ እኮ ነው፡፡ ማንም አሳልፎ የሚሰጠው ነገር የለም፡፡ በቃ 3 ነጥብ አጣን፣ ቦትስዋና ትወስደዋለች፡፡ ደቡብ አፍሪካን እንበልጣታለን፡፡ አስቀድሞ በነበረን እቅድ ከሴንትራል አፍሪካ ጋር ከምናደርገው ጨዋታ ሁለተኛውን ቡድን ለማሳለፍ ነበር፡፡ ያንን ማድረግ አንችልም፡፡ እስከመጨረሻው የማጣሪያ ጨዋታ ባለን ጊዜ ተጨዋቾችንን በሙሉ አቅም ሰብሰብ አድርገን አደራጅተን፣ በቂ ዝግጅት አድርገን መስከረም 6ቀን 2006 ዓ.ም ሴንተር አፍሪካን ገጥመን በማሸነፍ ለመጨረሻው የማጣሪያ ምዕራፍ እንገባለን፡፡

ለወደፊት የሚደገም ስህተት አይሆንም፡፡›› በማለትም ብሄራዊ ቡድኑ በውጤታማነት እንደሚቀጥልም በልበሙሉነት ተናግረዋል፡፡ ከአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ጋር በፌደሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ በሁለተኛ ደረጃ የተጠየቁት የቀድሞው የብሄራዊ ቡድን ረዳት አሰልጣኝ ስዩም ከበደ እና የስራ አስፈፃሚው አባል እና በደቡብ አፍሪካ እና ኢትዮጵያ ጨዋታ የቡድን መሪ የነበሩት አቶ አፈወርቅ አየለ ናቸው፡፡ አሰልጣኝ ስዩም ከበደ፣ ባለህ የዳበረ ልምድ እንዲሁም ከኮምፒውተርና ከኢንተርኔት ጋር በነበረህ የተሻለ ቅርበት የደቡብ አፍሪካው ጨዋታ ላይ የነበረውን የቢጫ ካርድ ጥፋት እያወቅህ በቅንነት አልተናገርክም በሚል ተገምግሟል፡፡ የቡድን መሪ የነበሩት አቶ አፈወርቅ አየለ ደግሞ በ2014 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ሲጀመር፣ የቡድን መሪ ሆነው በሰሩበት ወቅት፣ የፊፋ የውድድር ህገ ደንብ ተሰጥቷቸው ለሚመለከታቸው ባለመስጠታቸውና ለተጨዋቾች በቂ ግንዛቤ እንዲፈጠር ባለመስራታቸው እንዲሁም ለተተኪው የቡድን መሪ መረጃዎችን ባለማስተላለፋቸው በቅንነት መጓደል ጥፋተኛ ተብለዋል፡፡

የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ በ3ኛ ደረጃ ተጠያቂ ያደረገው ምንያህል ተሾመን ነው፡፡ ምንም እንኳን በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ በርካታ ጋዜጠኞች በተጨዋቹ ተጠያቂነት ላይ ፌደሬሽኑ የደረሰበት ድምዳሜ የልጁን ድካምና አስተዋፅኦ ከግምት አላስገባም በሚል ውሳኔው በድጋሚ እንዲጤን ግፊት ቢያደርጉም የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ሳህሉ ገብረወልድ ተጨዋቹ ለተፈፀመው ጥፋት የኢትዮጵያ ህዝብን በግልፅ ይቅርታ ሊጠይቅ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት፡፡ ምንያህል ተሾመ ለስራ አስፈጻሚው ስብሰባ ተጠርቶ ሊገኝ አለመቻሉን በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የጠቆሙት የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት፤ በተፈፀመው ጥፋት ተጨዋቹ በጣም ማዘኑንና መከፋቱን ከመገናኛ ብዙሃን መረዳታቸውን ገልፀው፣ ፌዴሬሽኑ ጥሪ ያደረገለት በጉዳዩ ላይ ለሚቀርብበት ጥያቄ ምላሽና ማብራሪያ እንዲሰጥ እንደነበረና እንደ ፕሮፌሽናል ተጨዋች ሙያውን አክብሮ ስህተቱ እንዳይፈፀም ባለመጠንቀቁ፣ እንዲሁም እኔ አይደለሁም ቢጫ ካርዱ የተሰጠኝ፣ አጠገቤ ለነበረው ለሌላ ተጨዋች ነው በማለት አሳማኝ ያልሆነ አስተያየት መስጠቱን ኮንነዋል፡፡ ዳኛ በቃሬዛ ለሚወጣ ተጨዋች እንኳን የካርድ ቅጣት ይሰጣል፡፡ አላወቅሁም አላስተዋልኩም ማለቱ አያሳምንም ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ ማሰብ ያለበት ለብሔራዊ ቡድን፣ ለአገራዊ ኃላፊነትና ግዴታ ነበር፡፡ ያለበትን ኃላፊነት ስነምግባራዊ በሆነ መንገድ አልተወጣም፤ ስለዚህም ተጠያቂ ነው ብለዋል፡፡ የፌደሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ በ4ኛ ደረጃ ተጠያቂ ያደረገው ጽ/ቤቱ እና ዋና ፀሐፊውን አቶ አሸናፊ እጅጉ ነው፡፡

የፌዴሬሽኑ ዋና ፀሐፊ አቶ አሸናፊ እጅጉ፤ በጋዜጣዊ መግለጫ መጀመርያ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫውን ማጣሪያ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ችግሩ እስከተፈጠረበት የቦትስዋና ጨዋታ ድረስ ያለውን የስራ ሂደት አስረድተው ነበር፡፡ “በማንኛውም ጊዜ በወንዶቹም በሴቶችም ብሔራዊ ቡድኖች የአፍሪካና የዓለም አቀፍ ውድድር በሚመጣበት ጊዜ ለፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት ኮሚኒኬ ይደርሰናል” ያሉት ዋና ፀሃፊው አቶ አሸናፊ እጅጉ፤ ኮሙኒኬዎች ሲደርሱ በቀጥታ የሚሰጣቸው አካላት አሉ፡፡ ኮሚኒኬዎች በተለያዩ የሰነድ ወረቀቶች ተደብቀው እንዳይቀሩ በአስቸኳይ ወዲያውኑ ለሚመለከተው አካል የምንሰጥበት አሰራር አለ በማለት ዝርዝር ማብራርያ አቅርበዋል፡፡ በአጠቃላይ ዋና ፀሐፊው የአራቱ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ግጥሚያዎች ኮሚኒኬዎች ከፊፋ ተልከው ወደ ፅህፈት ቤቱ በደረሱ ማግስት ለቡድን መሪዎች በማስፈረም፤ ኮሚኒኬው እንዲደርሳቸው መደረጉን በቀረን ማስረጃ አረጋግጠናል በማለት ለፅህፈት ቤቱ በኮፒ የቀሩ ማስረጃዎችንም አሳይተዋል፡፡

ጽ/ቤቱ ምን ማድረግ ሲገባው ምን እንዳላደረገ መግለጽ እንዳለበት የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ካሳሰቡ በኋላ፤ ዋና ፀሐፊው አሸናፊ ተጠያቂ ስለመሆናቸው በራሳቸው አንደበት እንዲናገሩ እድል በተሰጣቸው ጊዜ “ግዴታዬን በሚገባ ተወጥቻለሁ፣ ማስተዋል ነበረብህ ለሚባለው እያወቅሁ ያጠፋሁት አይደለም፡፡ ኮሙኒኬዎች ለቡድን መሪው በአስቸኳይ እንዲሰጥ አድርጌያለሁ፡፡ ተጨዋቹ ሁለት ቢጫ እንዳለበት አላየሁም፤ አለማስታወሴ ጥፋት ሊሆን ይችላል፡፡” በማለት አጠር ያለ ቃላቸውን ሲሰጡ፤ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ሳህሉ ዋና ፀሃፊው ለምን ተጠያቂ እንደሆኑ አብራርተዋል፡፡ ዋና ፀሐፊው ለፌደሬሽኑ ከፍተኛ አመራሮች እና ሃላፊዎች ትኩረት በመስጠት ደብዳቤዎችን ማድረስ ሲገባው፤ በጽሕፈት ቤት በኩል ወይም በፀሐፊው አማካኝነት ደብዳቤው ይሰጠው በሚል መስራቱ ትክክል አልነበረም ያሉት ፕሬዝዳንቱ ፤ አቶ አሸናፊ እጅጉ ተገቢውን የአሰራር ስነምግባር እና ስነስርዓት በመጠበቅ በስልክ ጠርቶ በአካል ተገናኝቶ ደብዳቤዎችን ለሚመለከታቸው መስጠት ሲገባው ይህን ባለማድረጉ ተጠያቂ ነው፡፡

ለዋና አስልጣኙም ይህን አላደረገም፡፡ ስለዚህ ጽ/ቤቱ በነፈገው ትኩረት ተጠያቂ ነው፡፡ ተገቢ የሆነ ክብርና ስነምግባር ባለመከተል ለተፈጠረው ችግር አስተዋጽኦ እንደነበረው በግምግማችን አምኖ ተቀብሏል በማለት አስረድተዋል፡፡ የፌደሬሽኑ ቀጣይ ተስፋ በጋዜጣዊ መግለጫው ከበርካታ የስፖርት ጋዜጠኞች የተነሱ ጥያቄዎች የፌደሬሽኑን ስራ አስፈፃሚዎች ያስጨነቁ ነበሩ፡፡ የፌደሬሽኑ ስራ አስፋፃሚ በጋዜጣዊ መግለጫው የደረሰውን ጥፋት በወረቀት መጥፋት ማሳበቡ፤ በጠቅላላው ስራ አስፈፃሚው ሙሉ ለሙሉ ተጠያቂ መሆን ሲገባው ግለሰቦችን በተናጠል ተጠያቂ ማድረጉ ተገቢ አለመሆኑን፤ የፌደሬሽኑ አሰራር የተበላሸ እና በአማተሪዝም የወደቀ መሆኑ ለችግሩ መንስኤ እንደሚሆን እንዲሁም ፌደሬሽኑ በሀምሌ ወር መጨረሻ ጠቅላላ ጉባኤ ያደርጋል ተብሎ ሲጠበቅ ይሄው ቀነ ቀጠሮ እንዲራዘምለት ስፖርት ኮሚሽን መጠየቁን በተመለከተ በተነሱ አንኳር ጉዳዮች እና አጀንዳዎች ላይ የፌደሬሽኑ አመራሮች ምላሾችንም ሰጥተዋል፡፡ የተሳሳትነው በርካታ ፈታኝ የውድድር ምእራፎችን በማለፋችን በተደራራቢ የእድገት እና የለውጥ ምእራፎች ስንቀሳቀስ በመቆየታችን ነው ሲሉ የተናገሩት አቶ ሳህሉ ገብረወልድ ‹‹በአጠቃላይ በውስጥ አካሎች ድክመት በፌዴሬሽኑ የተሰራው ስራ ሁሉ ጥላሸት ተቀብቷል፡፡ የኃላፊነትና ተጠያቂነት ስራ በየደረጃው ባለመፈፀሙ ለተፈጠረው ስህተት አዝነናል፡፡

በተጠያቂዎች ላይ ርምጃ ለመውሰድ ሰኞ የተደረገው የስራ አስፈፃሚ ስብሰባ በቂ ግዜ አልነበረም፡፡ ጊዜ ባለመኖሩ በተጠያቂዎች ላይ የሚተላለፈው ቅጣት አልተላለፈም፡፡ በተጠያቂዎች ላይ በየደረጃው በማድረጉ ስብሰባዎች የቅጣት ውሳኔዎችን እናስተላልፋለን›› ብለዋል፡፡ የፌደሬሽኑን አመራር በፕሮፌሽናሊዝም የአሰራር መዋቅር ለማጠናከር ስንቀሳቀስ ቆይተናል የሚሉት አቶ ሳህሉ ገብረወልድ፤ ባለፉት አራት አመታት የሰው ሃይል በማደራጀት፤ አሰራሮችን በማሻሻል የገቢ ምንጮችን በማስፋት ብዙ ተግባራት እንደተከነወኑ ገልፀው እውቀትና ችሎታ ያላቸውን ባለሙያዎች ከያሉበት አሰባስበን በእድገት እና ለውጥ ለመቀጠል በያዝነው እቅድ እንቀጥላለን ብለዋል፡፡ ፌደሬሽኑ ሃላፊነትን ወስዶ ተጠያቂነትን የሚሸሽበት ምንም ምክንያት የለም ያሉት የፌደሬሽኑ ዋና ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ተካ አስፋው ሲሆኑ የምንሰራው በጋራ አመራር ስለሆነ ሃላፊነት አለብን ሁላችንም ጥፋት ፈፅመናል እንጅ ጥፋት ፈፅመዋል አላልንም ሲሉ አስረድተው የትም አገር ላይ ስህተት ይፈፀማል፤ አምስት አገር ተሳስቷል፡ ብቸኛዎቹ እኛ ብንሆን ምን ሊፈጠር ነበር፡፡

ስህተቱን ማሳነስ አይደለም ብሄራዊ ቡድኑ 3 ነጥብ አሳጥተነዋል ለዚህ ሁላችንም ተጠያቂ ነን፡፡ በህግ አነጋገር ሆን ተብሎ ወይም በቸልተኝነት ጥፋት አለ፡፡ እኛ የሰራነው ስህተት ግን ሁለቱንም አይደለም ›› በማለት የፌደሬሽኑን ተዓማኒነት ለመከላከል ሞክረዋል፡፡ የደረሰው ጥፋት የተቋሙ ውድቀትን አያሳይም ድክመት ግን እንዳለ ቢያመለክት ነው ያሉት አቶ ተካ፤ አስቀድመው ከነበሩት ፌዴሬሽኖች የተሻለ ሰርተናል ፤ ለውጦችም አሳይተናል፡፡ ከደቡብ አፍሪካው 29ኛው አፍሪካ ዋንጫ ስንመለስ ህዝብ በደማቅ አቀባበል ነው የተቀበለን፡፡ ዋንጫ ስላሸነፍን አይደለም ጥሩ ተሳትፎ ስለነበረን ነው፡፡ ህዝብ ዳኝነት ያውቃል፡፡ አሁን በተፈጠረው ስህተት ህዝቡ ፌደሬሽኑን አይንህን ላፈር ይለዋል ብለን አንጠብቅም፡፡ 4 ዓመታትን ሰርተናል፡፡ ለ12 አምስት ጉዳይ በተፈፀመ ስህተት መኮነን የለብንም፤ የሚሰራ ነው የሚሳተተው እኛስ መጥኔ ለሚመጣው ፌደሬሽን ነው የምንለው›› በማለትም ተጨማሪ ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡

በአዲስ አበባ የሚገኙ ወጣቶች የሙዚቃ ምትን በመጠቀም መልእክት ማስተላለፍ በሚቻልበት መንገድ ሥልጠና ተሰጣቸው፡፡ ለሃያ ወጣቶች ለአስር ቀናት የተሰጠው ስልጠና በኢትዮጵያ ሲካሄድ የመጀመርያው መሆኑን ሥልጠናውን ያስተባበረው ኢንትራሄልዝ ኢንተርናሽናል - ኢትዮጵያ አስታውቋል፡፡ “ቢት ሜኪንግ ላብ” በተሰኘ በጀርባ ቦርሳ ሊያዝ የሚችል የሙዚቃ ስቱዲዮ በመጠቀም ስልጠናውን የሰጡት በአሜሪካ የሰሜን ካሮላይና ዩኒቨርሲቲ የሙዚቃ ፕሮፌሰሮች እና የተንቀሳቃሽ ስቱዲዮው መስራቾች ናቸው፡፡ በጤና ላይ የሚሠራው ኢንትራሄልዝ እና የዩኒቨርሲቲው የሙዚቃ ፕሮፌሰሮች ቀጣይነት ያለው ሥልጠና የወጣቶችን የሙዚቃ ክህሎት በማዳበር ወጣቱን በተዋልዶ ጤና፣ ኤችአይቪ/ኤድስ፣ በእናቶችና ሕፃናት ጤና እና በሌሎችም ማህበራዊ ዘርፎች የምት ሙዚቃ በመጠቀም ማስተማር እንደሚቻል ያሳየንበት ነው ብለዋል፡፡ ተማሪዎቹ ከትናንት ወዲያ ኮከበ ጽባሕ አካባቢ በሚገኘው የኢንትራሄልዝ ግቢ ሲመረቁ ለማስተማርያ የመጡት ተንቀሳቃሽ ስቱዲዮዎች ከወጣቶች ጋር ለሚሰሩት ለሚዩዚክ ሜይደይ ኢትዮጵያና “ሴቭ አወር ጀነሬሽን” ለተባለ ድርጅት ተለግሰዋል፡፡

በአስራት አብርሃም የተሰናዳውና “ፍኖተ ቃየል” በሚል ርእስ “የኢትዮጵያን ፖለቲካ ሽርፍራፊ ገፆች” የሚያሳየው መጽሐፍ ለንባብ በቃ፡፡ 199 ገፅ ያለው መጽሐፍ የተቃዋሚ ኃይሎችን አሰላለፍ፣ የርእዮተዓለማዊ ትግልን፣ ሕወሓትንና ሌሎችን የተመለከቱ ርእሰ ጉዳዮች አካቷል፡፡ የመጽሐፉ መሸጫ ዋጋ 45 ብር ነው፡፡ አዘጋጁ አቶ አስራት ካሁን ቀደም “መለስ እና ግብፅ”፣ “ከአገር በስተጀርባ” እና “ጎበዝ ተማሪ የመሆን ምስጢር” በተሰኙ መጻሕፍቶቻቸው ይታወቃሉ፡፡

Page 4 of 17