“ኬሮ” የተሰኘው የድምፃዊት ቢጢቅ እምላዕሉ የሙዚቃ አልበም ለገበያ ቀረበ፡፡ አስራ አራት ዘፈኖች የተካተቱበት አልበም መጠርያ ወላይትኛ ሲሆን አስሩ ዘፈኖች የአማርኛ፣ አራቱ ዘፈኖች ደግሞ የእንግሊዝኛ ናቸው፡፡ ሉሽስ መልቲ ፕሮዳክሽን አሳትሞ አምባሰል ሙዚቃ ቤት እያከፋፈለ የሚገኘውን አልበም ግጥሞች ማትያስ ይልማ፣ ዲጄ ዊሽ፣ ቤቲ ሮክ፣ ዳዊት ወርቁና ሌሎችም የፃፉት ሲሆን ዜማው በማትያስ ይልማ ተዘጋጅቷል፡፡ ሙዚቃውን ያቀናበሩት ደግሞ አቤል ጳውሎስ እና ኬኒ አለን ናቸው፡፡

በአውሮፓ የሚቸበቸበው የነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ሲዲ በአገር ውስጥ ገበያ ላይ የለም

ና ብትይኝ መጣሁ ብመጣ አንቺ የለሽ፣ ያመትባል ቤተስኪያን ሆኖ ቆየኝ ደጅሽ፡፡ ያመትባል ቤተስኪያን ሆኖ ቢቆይ ደጄ፣ ቆመህ አስቆርበህ ስመህ ሂድ ወዳጄ፡፡ ድምፃቸውን በሸክላ ለማስቀረፅ በአገራችን የመጀመሪያው የሆኑት የነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ግጥም ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነበት ምክንያት፣ 100 ዓመታትን ያስቆጠረው የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ሸክላ አስመልክቶ የተዘጋጀው በዓል ለምን ተቋረጠ የሚለውን ጉዳይ ለማንሳት ነው፡፡ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ የመጀመሪያው ሸክላ በነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ተዚሞ፣ እ.ኤ.አ በ1910 ዓ.ም በጀርመን አገር የተቀረፀው ሸክላ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ዘለሰኛና መዲና ዘፈኖች በአስራ ሰባት አይነት ስልት በመጫወት ድምፃቸውን በዲስክ ለማስቀረፅ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የሆኑት ነጋድራስ ተሰማ፣ በዘፈኖቻቸው የአገርና የባንዲራ ፍቅርን፣የተቃራኒ ፆታን ፍቅር ፣ስልጣንን፣ጀግንነትን አውድሰውበታል፡፡

ነጋድራስ ተሰማ፣ የመኪና ሹፍርናና የመካኒክነት ሙያን እንዲሰለጥኑ በአፄ ምኒልክ ተመርጠው ወደ ጀርመን አገር በተላኩ ጊዜ ከተላኩበት ሙያ ውጪ በስዕል፣ በቅርፃ ቅርፅና በሙዚቃ ሙያ በርካታ ስራዎችን ሲሰሩ ቆይተው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ቀራፂ፣ ፎቶግራፈር፣ አዝማሪ፣ ባለቅኔ፣ ሰዓሊ፣ የፖለቲካ ሰው፣ ነጋዴና የመኪና ጠጋኝና ሹፌር የሆኑት ነጋድራስ ተሰማ፣ በዘመናቸው በርካታ አዳዲስ ነገሮችን ለመጀመር ከፍተኛ ፍላጎትና ጉጉት የነበራቸው ሰው ነበሩ፡፡ ከዘፈን ችሎታቸው በተጨማሪ የተለያዩ ስዕሎችንና ቅርፃቅርፆችን በመስራት ለአዳዲስ ሙያዎች ፈር ቀዳጅ እንደሆኑም ይነገራል፡፡

ሃሳባቸውን በነፃነት ለመግለፅና ፊት ለፊት ለመጋፈጥ ደፋር ነበሩ የሚባሉት ነጋድራስ ተሰማ፣ የቅርፃ ቅርፅ ስራዎች፣ ስዕሎችና ዘፈን ከቤተክርስቲያን ውጪ ሀጢያትና ክፉ ስራ እንደሆነ ይታመን በነበረበት በዚያ ዘመን፣ የፍቅረኛቸውን ምስል በቅርፅ ሠርተውና የተለያዩ የፍቅር ዜማዎችን በማዜም ፣ ዘመናቸውን የቀደሙና ሃሳባቸውን በነፃነት ለመግለፅ የደፈሩ ሰው ናቸው፡፡ እነዚህን ከአንድ መቶ አምስት አመት በፊት በሸክላ ተቀርፀው የወጡትን የነጋድራስ ተሰማ እሸቴ የዘፈን ሥራዎች ለማግኘትና በቅርስነት ለመጪው ትውልድ እንዲተላለፉ ለማድረግ፣ የነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ልጅ የነበሩት ታዋቂው የስፖርት ሰው አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ለአመታት ደክመው ሊሣካላቸው ባይችልም አደራውን ለልጃቸው ለአቶ ታደለ ይድነቃቸው አውርሰው አልፈዋል፡፡

አቶ ታደለም እነዚህን ጥንታዊ የሙዚቃ ሸክላዎች ለማግኘትና በቅርስነት እንዲያዙ ለማድረግ አመታትን የፈጀ ድካምና ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ጥናት ኢንስቲትዩት ወዳጆች ማህበር፣ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ ላይ ባዘጋጁት አንድ ፕሮግራም በክብር እንግድነት የተጋበዙት አቶ ታደለ ይድነቃቸው፣ ስለ መጀመሪያዎቹ የኢትዮጵያ ሸክላዎች በመናገር ዘፈኖቹን ለታዳሚዎቹ አሰሙ፡፡ ይህ ጉዳይ የመሰጣቸው የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት፣ ለጀርመኑ የማይንዝ ዩኒቨርሲቲ የሙዚቃ ታሪክ ተመራማሪ ለዶክተር ዎልፍ ጋንግ ቤንዳር በማሳወቅ የዲስኮቹ ፍለጋ ተጀመረ፡፡ ፍለጋው ተሣክቶም በ1994 ዓ.ም 16 አልበሞችን የያዘ ሸክላ በኢትዮጵያ ጥናት ኢንስቲትዩት ዕቃ ማከማቻ መጋዘን ውስጥ ተገኘ፡፡ በዕድሜ ብዛትና በግዴለሽ አያያዝ የተጐዱትን ዲስኮች በመጠገን እንደገና እንዲቀረፁ ለማድረግ ዶክተር ዎልፍ ጋንግ ቤንደር፣ አቶ ተሾመ ደስታ የተባሉትን ሰው የቀጠሩ ሲሆን ዲስኮቹም ለመጀመሪያ ጊዜ እ.ኤ.አ ፌብሪዋሪ 2002 ዓ.ም ተቀረፁ፡፡

ይህ ቀረፃ ከተጠናቀቀ በኋላ አቶ ታደለ ድምፁ ጥራት እንዲኖረው በማሰብ ከአቶ ተሾመ ጋር በድጋሚ እንዲቀረፅ አደረጉት፡፡ የኢትዮጵያን የጥንት ሙዚቃዎችና ዜማዎች በዘመናዊ ዘዴ በማስቀረፅ ዕውቅና ያላቸው ፈረንሳዊው የሙዚቃ ሰው ሚስተር ፍራንሲስ ፋልሴቶ፣ እ.ኤ.አ በ2007 ዓ.ም በጃንዋሪ 2007 ዓ.ም ዲስኮቹን አስቀርፀው ለማሣተምና በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ አገራት ለማሰራጨት ፍላጐት በማሳየታቸው በጉዳዩ ዙሪያ ከአቶ ታደለ ይድነቃቸው ጋር ይነጋገራሉ፡፡ አቶ ታደለም በጉዳዩ ይስሙማና በቅጂ መብትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ስምምነት አድርገው ተጨማሪ የታሪክ ሰነዶችንና ፎቶግራፎችን ለሚስተር ፍራንሲስ ይሰጧቸዋል፡፡ ለሥራው የሚሆን የገንዘብ ድጋፍም ከዩኔስኮ ተገኝቶ የፈረንሳይ ኤምባሲ፣ ገተ ኢንስቲትዩት እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ባደረጉት ትብብር ሥራው ተሠርቶ ይጠናቀቃል፡፡ የምረቃ ፕሮግራም ወጥቶ የምረቃ ጥሪ ወረቀቶች ከተበተኑ በኋላ ፕሮግራሙ እንዲሰረዝ በመደረጉ፣ ታሪካዊ ሲዲ ምረቃው እንዳይካሄድና በአገር ውስጥም እንዳይሰራጭ ሆነ፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ታሪካዊ ሲዲዎች በተለያዩ የአውሮፓ አገራት በገበያ ላይ ቀርበው እየተቸበቸቡ ይገኛሉ፡፡

ታሪካዊ ዲስኮቹ የታሪካዊነታቸውና የቅርስነታቸው ባለቤት በሆነች አገር ውስጥ እንዳይሰራጭ ተደርገው፣ በውጭ አገራት እንደተራ የሙዚቃ ሲዲ እንዲቸበቸቡ የሆነበት ምክንያት ምንድነው የሚለውን ጥያቄ ለጉዳዩ ባለቤት ለአቶ ታደለ ይድነቃቸው አቅርበንላቸው ነበር፡፡ “እ.ኤ.አ. በ2007 ዓ.ም ሚስተር ፍራንሲስ ፍልሴቶ ዲስኮቹን ለማሳተም ሲጠይቀኝ ፍቃደኝነቴን የገለፅኩለት በደስታ ነበር፡፡ የነጋድራስ ተሰማ ቤተሰቦች ምንም አይነት የገንዘብ ጥቅም እንደማይፈልጉ፣ ሥራዎቹ ግን የኢትዮጵያ ህዝብ ንብረትና ቅርሶች በመሆናቸው የእኔ ነው ማለት እንደማይችል ተነጋግረንና ተስማምተን በህጋዊ ሠነዶች ላይም ይህንኑ ገልፆና ፈርሞ መረጃዎችንና ሠነዶችን ሰጠሁት፡፡ ሠነዶቹን ከወሰደ በኋላ፣ ከዩኔስኮ የገንዘብ ድጋፍ አግኝቶ ሥራውን ሠርቶ አጠናቀቀ፡፡ ሲዲውን ለማስመረቅና ወዲያውም የመጀመሪያውን ኢትዮጵያዊ ሸክላ አንድ መቶኛ አመት ለማክበር ፕሮግራም ለማዘጋጀት ማሰቡን ሲነግረኝ ሲዲውን እንዲልክልኝና እንዳየው ጠየቅሁት፡፡ ሲዲውን ሲልከው በጀርባው ላይ የቅጂ መብቱንና የባለቤትነት መብቱን የራሱ አድርጐ አሣትሞታል፡፡

በሁኔታው አዝኜ የሠራኸው ሥራ ከውልና ከስምምነታችን ውጪ በመሆኑ፣ የቅጂና የባለቤትነት መብቱን በአስቸኳይ አንሣ ብዬ ፃፍኩለት፡፡ ይቅርታ ጠይቆኝ እንዳነሣው ገልፆ በድጋሚ ላከልኝ፡፡ ሣየው በጀርባው ላይ ያለው ነገር ተነስቷል፡፡ ደስ ብሎኝ ፕሮግራሙ እንዲቀጥል ነገርኩት፡፡ ፕሮግራሙ በጐተ ኢንስቲትዩት እንዲሆን ተስማምተን በምረቃው ላይ መገኘት ይገባቸዋል ለተባሉ ሰዎች የጥሪ ወረቀት እንዲደርስ ተደረገ፡፡ እኔም በፕሮግራሙ ላይ በክብር እንግድነት እንድገኝና ንግግር እንዳደርግ ተጋበዝኩ፡፡ እሺ ብዬ በዕለቱ የማደርገውን ንግግር ለማዘጋጀት ማጣቀሻ የሚሆን መረጃ ፈልጌ ሲዲውን ስከፍተው፣ የሲዲው የቅጂ መብትና ሙሉ ባለቤትነቱ የቡድሃ ሚዩዚክ መሆኑን የሚገልፅ ፅሁፍ በሲዲው ላይ በግልፅ ተፅፏል፡፡ ሲዲውን ከቡድሃ ሚዩዚክ ፍቃድ ውጪ ማንም ሰው ማሣተም፣ ለህዝብ ማሠማት አይችልም ይላል፡፡ ምን ማለት ነው? ንብረቱ እኮ የኢትዮጽያ ህዝብ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት እኔ በፕሮግራሙ ላይ እንደማልገኝ አሣወቅሁኝ፡፡ በጉዳዩ የፈረንሳዩ አምባሳደርና ሌሎች ሰዎች ገብተው ሊያነጋግሩን ሞክረው ነበር፡፡ እኔ የቅጂ መብቱን በማንኛውም መልኩ በየትኛውም ስም አላስመዘገብኩትም ብሎ ከፈረመልኝ ምረቃው ሊቀጥል ይችላል አልኩ፡፡ ሚስተር ፍራንሲስ ግን ለዚህ ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ ይህ ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ሥራዎች ላይ ጥናት የሚያደርጉትን ተመራማሪዎች በነፃነት እንዳይሰሩ የሚያደርጋቸውና ምርምራቸውን ለማቆም የሚያስገድዳቸው ጉዳይ ነውና እኔ በዚህ ፈፅሞ ልስማማ አልችልም፡፡ ከሚስተር ፍራንሲስ ጋር በተደጋጋሚ የተነጋገርን ቢሆንም ልንስማማ አልቻልንም፡፡ በአውሮፓ የተለያዩ አገራት ስዘዋወር ሲዲዎቹ እንደማንኛውም ተራ ሲዲ በየሙዚቃ ቤቶቹ መደርደሪያ ላይ ተደርድረው እየተሸጡ ነው፡፡ ይህ በጣም የሚያሣዝን ተግባር ነው፡፡

ሥራዎቹ እኮ ቅርስ ናቸው፡፡ እኔ አሁን ሥራዎቹን በስሜ ለማሣተምና የቅጂ መብቱን ወስጄ ለሌሎች በሥራዎቹ ላይ ጥናትና ምርምር ለሚያደርጉ ሁሉ በነፃ ለመስጠት ወስኛለሁ፡፡ የእኔ ፍላጐት ጥናቱ እንዲቀጥል ነው፡፡ ሸክላዎቹ የአገር ቅርስ ናቸውና፡፡ ሚስተር ፍራንሲስ ፋልሴቶ እነዚህን ሲዲዎች በሌላ ሰው (ድርጅት) የቅጂ ባለቤትነት መብት ለማስመዝገብ ምን መብት አላቸው? ከውልና ከስምምነቱ ውጪስ ለመሥራት ለምን ተነሳሱ የሚሉና ሌሎች ጥያቄዎችን ለመጠየቅ ሚስተር ፍራንሲስ ፋልሴቶን ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ “በአገር ውስጥ የሉም” በሚል ምክንያት ሳይሳካልን ቀርቷል፡፡ ሚስተር ፍራንሲስ ምላሻቸውን በሰጡን ጊዜ ልናስተናግዳቸው ዝግጁ መሆናችንን በዚሁ አጋጣሚ ለመግለፅ እንወዳለን፡፡

Published in ጥበብ
Saturday, 22 June 2013 12:02

እማይነትበዉ ስዉር-ስፌት

“ሰዉ ባገሩ በወንዙ ማበድ መወፈፍ ካልቻለማ / ምን አገር ሆነ ያማ!” ጥበበኛ እንደልቡ ከገጠመኝ ለመሟገት፣ ዕዉነታዉን ቦርቡሮ የብርሃን ጭላንጭል ለመለጠጥ ያፈነግጣል፤ ርዕይ ይቋጥራል። “እንበድ” ሲል አረጋዊ እንደ መፈንከት ሳይሆን መገጣጠምን፣ የሃሳብ ወረርሺኝና - conformity - ከበባን እንደ መናድ ነዉ እንጂ።

ሂሳዊ ንባብ 
ክፍል ሶስት፥ የነቢይ ገሃድዘለል -
surrealistic - ግጥሞች
የነቢይን ግጥሞች ከማሰሴ በፊት ለመግባባት ሁለት እርከኖች መራመድ አለብኝ:: አንድ፥ surrealism ምን ማለት ነዉ? ሁለት፥ በአማርኛ ሥነፅሁፍ እነማን ወከሉት ? በደምሳሳዉም ቢሆን መልስ ይሻሉ። መንደርደርያዉ፥ በዚህ ስልት የተፃፉትን የነቢይ ግጥሞች ለማጣጣምና ለመገንዘብ እጅጉን ይበጃል።

ስያሜዉ
የ surrealism ገራገር ትርጉም ከዕዉነታ በላይ ማለት ነዉ። sur - ዲበ፣ በላይ ወይም ባሻገር፣ realism ዕዉነታነት። ለማቅለል ገሃድዘለል ማለትም ይቻላል። ዲበዕዉነታ በሃያኛ ክፍለ ዘመን በፈረንሳይ የተከሰተ የጥበብና የስነፅሁፍ ስልት ነዉ፤ እንደ አንድ ንቅናቄም ይጤናል። ያልተለመደና የማይታመን ምስል በመቀሸር ህልምንና ኢንቁ - unconcious - ገጠመኝን ለመወከል ይጥራል። ከህልም፣ ከረቂቅ ራዕይ፣ ከእብደት፣ ከሰመመን፣ ከቅዠት ... ምስልና ሁነት ይጐነጉናል። ሆኖም ለመንፈሳዊ ህይወት መኖር ማረጋገጫ ሳይሆን፣ ግባቸዉ ንቃታችንን በማክረር ዓለምን መለወጥ ነዉ። ህልማዊ ምስልን ያባብላሉ፤ ከዕዉነታና ከህልም ቀላቅለዉ ይፅፋሉ። የሚጋፉ ቃላትና ቁሳቁስ በማጐራበት - juxstaposition - የሚያስጐመጅ ምስል እና ህብሩን የሚለዋዉጥ ቃላዊ ዉጤት ያስገኛሉ። አንድ ሀያሲ እንዳለዉ የድንጋይ ከሰል ማዕድንና ቦምብ ማጐራበት። አንድ ፍካሬዉ በማዕድን ጉድጓድ ፅልመት አቅጣጫ የሳተ ግለሰብ፣ የቦምብ ፍንዳታ ብልጭታ ለአፍታ ያጥበረብረዋል ሊሆን ይችላል።
ገሃድ-ዘለልነት በሥነፅሁፍ ብቻ ሳይሆን በሙዚቃ፣ በስዕልና በሲኒማም ዐዉድ ይከሰታል። የልብስ ስፌት መኪና እና ዣንጥላ ከመክተፍያ ጠረጴዛ ላይ ማጋደም የመሰለ ትዕይንት፤ ገሃድ-ዘለሎች የማይጣጣም ቁሳቁስ በማጐራበት የፊልም ተመልካችን ማወክ ይሻሉ ትላለች Susan Sontag፥ Against Interpretation በሚለዉ መፅሃፏ። ፅንሰሃሳቡን በቀላሉ መጦቀም ይቻላል። “ትንኝም ለሆዱ፥ ዝሆንም ለሆዱ እወንዝ ወረዱ” ይህ ምሳሌያዊ ንግግር ደጋግመን ስለሰማነዉ ዶለደመ እንጂ ካጤኑት ይናደፋል:: የዝሆንና የትንኝ ጐን ለጐን መሄድ
- juxtapose - ልብ ካልነዉ የማይሆን ምስል ነዉ። በርሜል የሚሞላ ዉሃ ለመምጠጥ ኩምቢ ያለዉ ዝሆን ወንዝ ሊወርድ ይችላል፤ ትንኝ - ጭልፋ ዉሃ የሚያሰምጣት - ግን ጠብታ ፈሳሽ ከአካባቢዋ አታጣምና ወንዝ ደመኛዋ ነዉ። ይህ ገሃድዘለል ምስል ግን ሰዉ ለዕለት ኑሮዉ፣ ትንሹም ትልቁም እንደሚዳክር የጐላበት ነዉ። absolute reality ፍፁም ዕዉነታ ይሉታል። “ላም አለኝ በሰማይ፥ ወተቷን የማላይ” ይህ ከህልም፣ ከቅዠት የፈለቀ ምስል፣ ከዕዉነታ በላይ ነዉ፤ ጥልቀት አለዉ፤ የኛ እየመሰለን፣ ከመዳፋችን ያልገባ አልያም የህልም እንጀራ ሲደበዝዝ፣ እየተደናገርን ኑሮ ላይ ምላሳችንን አዉጥተን ለመዝለቅ እናፌዛለን። ትዝብትም ነዉ። “ድሃ በህልሙ ቂቤ ባይጠጣ፥ እከክ ይጨርሰዉ ነበር” ይህ መራር ዲበዕዉነታ ምስል ነዉ። ንቁ አዕምሮ የገደበዉን ድንበር በማፍረስ፣ ኢንቁ ህልም የመሰለ ምኞት ዉስጥ በመንሳፈፍ ሽንብራ ቆረጣጥሞ የሚያድረዉን፣ ቅቤ እንደ ካህን ትንቢት የራቀዉን ሰዉ፣ የቆዳዉ ልስላሴ በምን ይደረስበት? ህልም ከዕዉነታ በላይ ይጐተጉተናል። በዚህ ፈለግ ገድለ ሰማዕታት፣ የግዕዝ ቅኔና ተረቶቻችንን መቃኘት ብንጀምር፣ ለብዙ የፈረንጅ ... ism ማንፀርያ የሚሆን የሚፈለፈል ትዉፊት አናጣም። ለመቋጨት አንድ ዝነኛ ገሃድዘለል ስዕል እንመልከት። The Persistance of Memory [የትዉስታ እልህ] ዕዉቁ Salvador Dali የሳለዉ ነዉ።
ብዙ የተባለለት ገሃድዘለል ስዕል ነዉ። እንደታጠበ ፎጣ ርሶ የሚያንጠባጥብ የኪስ ሰዓት፣ ወይም እንደ አይብ ለስልሰዉ መቅለጥ የጀመሩ ሰዓቶች፤ አንደኛዉ እንድያዉም መሽተት የጀመረ ዳቦ ይመስል ጉንዳን ወረዉታል። ይህ ከኢንቁ አዕምሮ የተንሳፈፈ ህልማዊ ምስል ነዉ። አንዳንዶቹ ሲተረጉሙት እነዚህ እርጥብ ቀላጭ ሰዓቶች የጊዜን ግትርነትና አይበገሬነት አለመቀበልን፣ ለተሻለ ገሃድ መታከትን ያደምቃል ባይ ናቸዉ። ጥልቅ ትንታኔዉን ለሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህና ለሰዓሊ በቀለ መኰንን መተዉ ይመረጣል። እንድያዉም ሰዓሊ እሸቱ፥ የገብረክርስቶስ ደስታን ሥዕላዊ ዘይቤን ሲተነትን የጥበብ ገላጭነትን አራት ጠገግ ተጠቅሞ አምስተኛዉን ገሃድ-ዘለልነትን ግን አልሞከረም ይላል። እሸቱ surrealismን ሕልም-እዉነታነት ብሎታል፤ ለስዕል ይስማማል። [የኢትዮጵያ ጥናት መፅሔት፥ ቅፅ 37 ቁ2 ፥ ገፅ 62-63 ] መስፍን ሀብተማሪያም የደበበ ሠይፉን ለራስ የተፃፈ ደብዳቤ የግጥም ስብስብ ሽፋን የሳለዉ ድንቅ በሆነ ዲበዕዉነታ እሳቦት ነዉ። የDaliን ለስላሳ ቀላጭ ስዕሎች ያስታዉሰናል። የተጓዥ ጥላ በሰዉየዉ ኩታ ጫፍ ታስሮ ብድግ ብሎ ሊከተለዉ፣ ከዝርግነት ለማቅናት የሚጣጣር የተማፅኖ እንቅስቃሴ ነዉ።

ገሃድዘለል ስልት በአማርኛ ሥነፅሁፍ፥ እንደ መግቢያ
አንዳንድ የስብሀት ገ/እግዝአብሔር አጫጭር ልቦለድ ከህልም ከቅዠትም ተነስተዉ እንደ “አጋፋሪ እንደሻዉ” እንደ ”ስምንተኛዉ ጋጋታ” የገሃድ-ዘለልነት ጠባይ ታይቶባቸዋል። የአበራ ለማ “እቴሜቴ” አጭር ልቦለድ ገሃድና ቅዠት ተቀላቅሎባት፣ መገለል የጐዳት፣ ሥጋት የከበባት ገፀባህርይ ተቀርጾበታል። ላባቸዉ እላያቸዉ ላይ እንደ ጢስ በኖ ካለቀ ሁለት ዶሮዎች ትመካከራለች። ህፃኑ አኝኮ የጣለዉን ኮክ አንስታ “... ደጋግማ አገላብጣ አየችዉ። ቋንቋ ኖሮት ድምፅ አዉጥቶ ባያናግራትም፣ በፀጥታዉ አንድ ነገር እንደ ነገራት ሁሉ፣ ካካ!... ብላ ሳቀች” [የማለዳ ስንቅ፥ ገፅ 77] ከዕዉነታ በላይ፣ ኢንቁ አዕምሮዋ ዉስጠቱ የተበረበረበት ድንቅ ልቦለድ ነዉ።
አዉግቸዉ ተረፈ ታሞ ያዝ ለቀቅ ሲያደርገዉ እብደት ዉስጥ እያለ የፃፈዉን ስንዱ አበበ ከስር ከስሩ በመሰብሰብ ለመጀመሪያ ጊዜ በአማርኛ ሥነፅሁፍ ገሃድዘለሎች እንደሚሉት ያለንቁ የአዕምሮ ቁጥጥር በ - automatism - ጥበብ የተፃፈ ልቦለድ አስነብባናለች። “ህልም ማየት ስጀምር ነብይ የሆንኩ መሰለኝ። ... አንድ ቤተክርስትያን አገኘሁ። ደረጃዉ ላይ ጠጅ ይሸጣል። ጠጅ ቀጂዉ ራሱን ተላጭቷል። እዉስጥ እየተቀደሰ እሱ ጠጅ ይቀዳል። እኔ ስገባ ብርጭቆ አቀረበልኝ እና ሊቀዳልኝ ሲል ጠጁ ብርጭቆ ዉስጥ አልገባ ይለዋል። ሌላ ብርሌ ያመጣል ...” [እብዱ፥ ገፅ 7+8] ገፀባህሪዉ ከንቁ አዕምሮዉ ተላቆ በየቀኑ የሚገጥመዉን ፣ ያዝ-ለቀቅ እያደረገዉ የፃፈዉ ያስደምመናል። ደምሴ ፅጌ በፍለጋ ልቦለድ ቅድስት በማኅበራዊና በወሲባዊ ጥሪ ተወርራ አዕምሮዋን መቆጣጠር ሲሳናት ይህን ዉስጣዊ ጭንቀት የተገለጠበት ትዕይንት ገሃድዘለላዊ ነዉ። የበዕዉቀቱ ልቦለዶችም ሲጤኑ - በተለይም ዕንቅልፍና ዕድሜ - በህልም፣ በምኞትና በዕዉነታ የፈሉ ምስሎች አሉት።
ዛሬ ዛሬ ማኅበራዊ ድረገፅ - እንደ facebook - ለአማርኛ ወጣት ፀሐፍት ግጥሞቻቸዉን የሚያስነብቡበት ዐዉድ ለገሳቸዉ፤ ይወያዩበታል። ሄለን ካሣ “ቅጥሩ ግንብ ነዉና እምነ በረድ ቤት / መቼ ይታየኛል ! የነዋሪዉ ሞት” ስትል ነፍሱ የፈረጠችበት የተፈረካከሰ ገላ እና የማይገጣጠም ደማቅ መቃብር ጐን ለጐን ስታነፃፅር - juxstapose - ሰዉ በትዕቢት ይሆን በብስለቱ መሻሸር ስንት እሚያስጨንቅ እያለ በተራነት መጠመዱ አስገርሟታል። እንደ መኖሪያ ቤትም ከተጤነ አርቆ አለማሰብን ያንፀባርቃል ምስሉ። ለአንድ አመት ያክል ወጣቶች በየድረገፁ እየተቀባበሉ የዘመሩት ግጥም የበረከት በላይነህ “የህልሜ ደራሲ”ን ነዉ።
ስ ስምሽ ስላደርኩ ትላንት በህልሜ
ዛሬ ቶሎ ተኛሁ ልስምሽ ደግሜ፤
ታድያ ምን ያደርጋል !
የህልሜ ደራሲ አትታደል ቢለኝ
ህልሜን ገለባብጦ ሲስሙሽ አሳየኝ።
ይህ ለገሃድዘለል የአፃፃፍ ስልት ዐይነተኛ ምሳሌ ነዉ። አንድም፥ ኢንቁ የአዕምሮን ምኞት ህልም ዉስጥ በመዋኘት ማስገር ነዉ። አንድም፥ ክህደትን አልያም የታፈነ ፍትወታዊ ረሃብ ተናጋሪዉን ሲኮሰኩሰዉና ሲወረዉ እንደ ማምለጫ ህልምን ይማጠናል። አንድም፥ ኑሮ እኛ ባቀድነዉ ብቻ ሣይሆን የሆነ ኀይል ቱቦ እየቀደደ አቅጣጫ ማስለወጡን የመሰለ እሳቦት። ዋናዉ ግን በረከት ይፀዳ መስሎት ህልም ዉስጥ በዘፈዘፈዉ ግጥሙ የወጣቱን ስነልቦናና ፍላጐት፣ ይህን ፈጣን ንዝረት በመቀንበቡ፣ ምናብን አደፍርሶ ከዕዉነታ የላቀ የታመቀ ብዥታ መግራት መቻሉ ነዉ። ገሃድዘለሎች ከንቁ የአዕምሮ ቁጥጥር የማላቀቅ አርነት የሚሉትን አፈፍ ያደረገ ነዉ።
አዳም ረታ ለአማርኛ ልቦለድ የአፃፃፍ ክህሎት ሆነ የትረካ ስልት ፋና ወጊ - avant grade - እና ፈር ቀዳጅ ነዉ። ይህ ሂሳዊ ንባብ ለነቢይ ግጥሞች የተመደበ ነዉና ለገሃድዘለል በተለይም ዕዉነታን ለተሻገረ አንድ ድርጊት ከአዳም ልቦለድ ልጦቅም። መዝገቡ በልጅነቱ ወንዝ ዳር ያገኛት ድንጋይ “በጣቶቼ ስዳብሳት ነጭ ላባ እንደለበሰች ጫጩት የምትለሰልስ ነበረች። ያኔዉኑ ፍቅር ነገር ከእሷ ይዞኝ ...” የሚላትን ወደ ሰማይ ሲወረዉራት ሳትመለስ ቀረች። ከአመታት በኋላ ትዳር መስርቶ ቤተሰባዊ ፍቅር እየሞቀዉ ሳለ “ዐይኖቼን ወደ ቀኝ ስወረዉር መድረቅ የጀመሩ ሳሮች መሐል ያቺን ነጭ ድንጋይ አየሁዋት” ወደ ላይ ሊወረዉራት ሲል ምስትየዉ ከእጁ ላይ በፍጥነት አንስታት ተደመመች። “ ደስ አትልም? ሰዉ የሰራት ትመስላለች ... ከእጅዋ ተቀበልኩና ከእስዋ ፈቀቅ አልኩ። እዉስጤ የሆነ እምነት ነበር። ሕይወት ወፈረም ቀጠነም ዞር ብለን ስናየዉ የሆነ አስማትና ተአምር አለዉ። ሁሉ ክፉም ደጉም ከዉስጡ የተወሰወሰ ቶሎ ራሱን ከፍቶ የማያሳይ ተአምር አለዉ። ድንጋይዋን ... ወደ ላይ ወረወርኳት። ወደ ሰማይ በግምት አሥር ሜትሮች ያህል እንደተነሳች ... አንጋጠን እያየናት ጠፋች። ... ድንጋይዋ አልተመለሰችም:: [ግራጫ ቃጭሎች፥ ገፅ 50 + 440-442] እንዴት ሊሆን ቻለ? ይህ ዲበዕዉነታ ትዕይንት የልቦለዱን የተረክ ጥበብና የመዝገቡን ዉስጣዊ ህይወት እንዴት አበለፀገዉ? አስማትና ተአምርስ?
ደበበ ሠይፉ፥ ወጣቱ በሰመመን መለከፉንና ልቡ ዉስጥ ጨለማን ማጠራቀም መጀመሩን ተገንዝቦ የተቀኘዉ አንድ አሳሳቢ ገሃድዘለል ግጥም አለዉ። ዕፀ ፋርሱን በማሽተት ወደ ኢንቁ አዕምሮዉ የዘቀጠዉን የሳለበት።
እንደ ባዕድ አካል
ተገንጥሎ ሲሄድ ራሱ ከራሱ
እጆቹ እያጠሩ
አቅቶት ሲቸገር መዳበስ ማበሱ
እያደገ ሒዶ
የገዛ አፍንጫዉ ይላጋል ከአድማሱ! [የብርሃን ፍቅር፥ ገፅ 93]
በአማርኛ ስነፅሁፍ በ surrealism ስልት አስቦበት የፃፈዉ ሰለሞን ደሬሳ ነዉ። በወቅቱ የረጋዉን ሥነግጥም የበጠበጠዉ አርባ አራት ተኩል ግጥሞች በማለት ልጅነትን ያሳተመ ጊዜ ነበር። ለመፅሃፉ የመረጠዉ ጥቅስ ከዝነኛ ፈረንሳዊ ገሃድዘለል ገጣሚ Paul Eluard የተቀዳ ነዉ። “እረፍት በጠጠርና በእሾህ መድቦች / ላይ መገቻዉን አገኘ”። የመጋቢት 23/ 1992 አዲስ አድማስ፣ ሰለሞን በ1959 መነን መፅሄት ላይ የፃፈዉን አስነብቦናል። “ወረድ ብዬ ሁለት የራሴን ግጥሞች አቀርባለሁ። “ዘላለምሽ” የሚለዉ ከተለመደዉ የአማርኛ የወል ግጥም እምብዛም አይርቅም ... ረዘም የሚለዉ “ኤዉሮፓ” ግን ኬላ ሰባሬ ብጤ ሳይሆን አይቀርም። የሞከርኩት ኤዉሮፓዉያን ሱሪያሊዝም (ባማርኛ ከዕዉን በላይ ልንለዉ ይፈቀድ ይሆናል) የሚሉት አይነት ግጥም ነዉ። “በባህላችን ያሉት የግጥም ዓይነቶች መች አነሱንና!” ለሚሉት አንባቢዎች “አይበቁንም” ብዬ ያላንድች ጥርጣሬ እመልሳለሁ። ኤዉሮፓዉያንም የኛን የቅኔ ሥርዓት ቢያዉቁት ምነኛ በጠቀማቸዉ። በዚህ ዓለም ላይ ራሱን ችሎ ከጐረቤቱ ብድር የማያስፈልገዉ ህዝብና ሥልጣኔ አለ ብዬ አላምንምና።
ሸክላ ተሰብሮ ፍልጥ ጥርሱ ሲዳም
ዉሽማዬ ቁጭ ብላ በጐን ታለቅሳለች።
እንዳለቀ ሻማ ፍቅር ሲያቅማማ
አይኗ ተቀዶ ጥቁር ዉሃ ሲያፈስ [... እያለ ይቀጥላል ልጅነት፥ ገፅ 17]
ሌላም ሌላም መጥቀስ ይቻላል። የነቢይ ዲበዕዉነታ ግጥሞች ግን ማራኪና ላቅ ያሉ ናቸዉ።

የነቢይ ገሃድዘለል ግጥሞች
“ነፃነት ለጠማቸዉና ተባብረዉ ማበድ ለተሳናቸዉ ያገር ልጆች” በማለት ነቢይ የዛሬ ሃያ አመት “ኧረ እንበድ ጐበዝ” በሚል ግጥሙ ልክ እንደ ገሃድዘለሎች ከንቁ አዕምሮ ተፅዕኖ ለማፈትለክ ጥሪዉን ዘምሯል። “ሰዉ ባገሩ በወንዙ ማበድ መወፈፍ ካልቻለማ / ምን አገር ሆነ ያማ!” ጥበበኛ እንደልቡ ከገጠመኝ ለመሟገት፣ ዕዉነታዉን ቦርቡሮ የብርሃን ጭላንጭል ለመለጠጥ ያፈነግጣል፤ ርዕይ ይቋጥራል። “እንበድ” ሲል አረጋዊ እንደ መፈንከት ሳይሆን መገጣጠምን፣ የሃሳብ ወረርሺኝና - conformity - ከበባን እንደ መናድ ነዉ እንጂ።
ዜጋ አብዶ ገዱ ተንጋዳ
ነካ ነካ ካላረገዉ፣ በገዛ አገሩማ ጓዳ
ቢሻዉ ካልተሸማቀቀ፣ እገዛ ቤቱ እንደእንግዳ
ወይ ከት ከት ብሎ ካልሳቀ፣ አሊያም ድንገት ካልተቆጣ
ወፈፍ ወፈፍ ካላረገዉ፣ የእብደት አብሾ እንደጠጣ፤
እንዲህ እንዲያ ካልሆነማ
ምን አገር አለዉ እሱማ። [ጥቁር ነጭ ግራጫ - ገፅ 8]
ጥልቅ እሳቦት ሲመዘምዘዉ፣ ተለምዶ አልመጥነዉ ሲል ነቢይ ያፈተልክና ከዕዉነታ የላቀ ግጥም ይቀኛል።
ዕድሜዬን በሙሉ
በአፌ ፈረስ ልጓም
እጄ ላይ ሰንሰለት
ሲያኖሩ ስላየች፤
ፀሐይ ሰማይ በቅቷት
ዉሃ ሰጥማ ሞተች።
ዉሃ ዉስጥ ተኝታ
ከኔ ትዋሳለች፣ ይኸዉ ብርሃን አጥታ። [ስዉር-ስፌት፥ ገፅ 137]
ነቢይ የህዝባዊ ታጋይን ፅናት ለመፈልቀቅ ከህልም መዋስ አለበት፤ ከኢንቁ አዕምሮ ጠልቆ ምስል ያጠነፍፋል። ግለሰብ ሲታሰርና ሲታፈን ለአመታት አስተዉላ፣ እሱ ተስፋ ሳይቆርጥ ፀሐይ ብሶባት ከዉሃ ትሰጥማለች። ብርሃን አጥታ ትዋሰዋለች። ለወገናዊ ዓላማ በየዕለቱ ሲገጣጠብ ያልተሸነፈ ታጋይ፣ ገጣሚዉ እስከ ታህተንቃቱ ለመቆፈር ደፈረ - የብርታቱን ምስጢር ሥራስሩን ለመማስ። ፀሐይ ቢደርስባት የማታዝለዉ እንግልት፣ እሱን ከጨለማ አልዘፈቀዉም። ገላዉ ብርሃን ተርፎት ለሌላዉ ያበድራል::
በንቁ አዕምሮ ቢጤን የማይመስል ብቻ ሳይሆን፣ አለመምሰሉንና ቅዠት-አከል እንቅስቃሴዉ ወኔ የሚቦካበት ቡሃቃን ጠፈጠፈ። እንዲህ ነዉና ዲበዕዉነታዊ አፃፃፍ። “ዋሽ ቢሉኝ እዋሻለሁ፣ ነፋስ በወንፊት እይዛለሁ” ሳይሆን የግለሰብን ዉስጠት የመቧጠጥ ልክፍት እንጂ። የዕለት በዕለት የኑሮ ደለል የሸፈነዉን ግለሰባዊ፣ ህይወታዊ እንግልትና ወኔ፣ ህልማዊ ምስልን በማቀጣጠል ቦግታን መጫር ይቻላል። ይህ ዕድሜ እኮ፣ ከዉስጡ የታጐረ የአመታት ጠጠሮች ይርመሰመሱበታል። ገጣሚዉ ኅቱም ገጠመኝን መቀኘት አለበት - “ሙሴ የህዝበ እስራኤልን ዉሀ ጥም ለማብረድ ዉሀ ከፈለቀበት ኅቱም ድንጋይ” ድንግል ትዕይንት እንደማለት። የሚሸሽጉት ሳይሆን እንደማቅ የሚደርቡት ገመና። ይህ ከኢንቁ አእምሮ ለመግባት መፈርፈር፣ ህልምን መሸርሸር፣ ዕዉነታዉ ሽፋኑ ብቻ እንደማይታመን ክርስቶስም አስተምሯል።
“የበግ ለምድ ለብሰዉ ይመጣሉ፤ ዉስጣቸዉ ግን ተኩላ ነዉ” ነቢይ ግን በዚህ ግጥም ዉስጡ በተስፋና በወኔ የራሰዉን ነዉ ቅዠት ለዉሶ የተቀኘለት። “አዲስ ነገር ለመፍጠር፣ ... አሮጌ አብራክ የማስፈለጉን ያህል፣ አዲስ አተያይ ይዞ አዲስ ጥበብ መዉለድም ያሻል” ብሏል ነቢይ በመፅሐፉ መግቢያ። ከዕዉነታ በላይ በህልም ድንኳን፣ ገሃድዘለል ምስሎች እንደ ችግኝ የፈሉት ነቢይ ለሎሬት ፀጋዬ ህልፈት ሲቀኝ ነዉ። “ክረምት አለወሩ ገብቶ፥ ... ፀሐይ አለሰዓት ጠልቃ፥ ... ጨረቃም ጥቁር ሻሽ አስራ፥ ... ” ለፀጋዬ ቀብር ከመሬት ይወርዳሉ።
ከዋክብት አሸርጠዋል፣ የብርሃን ደረት ጥለዉ
በእድር አዉቶቡስ፣ ምድር ወርደዉ
“አስታዋሻችን ሞቶ፣ ሰማይ ምናችን ነዉ” ብለዉ
ቀብር አለብን ይላሉ፣ መቃብር ያለህ መስሏቸዉ
ያንተኮ ልዩ ማዕረግህ
ያለመቃብር ማረግህ። [ገፅ 29]
መንደሩና አካባቢዉ አልበቃ ብሎ ነቢይ ከአንጀቱ ሲያዝን ምናቡ ወደ ህልምና ቅዠት ተሰደደ። ደብዝዞ፣ ቀዝዞ ለመስለምለም ሳይሆን አንድ ትልቅ ሰዉ ሲገረሰስ እንዴት ሰምና ወርቁን ይለየዉ ? እነዚህ ገሃድዘለል ምስሎች ዕዉነታዉ እንዲፈጀን፣ እንዲለበልበን አግዘዉታል። ነቢይ ዲበዕዉነታ ስልትን የተገለገለዉ ኮስተር፣ ኮምጠጥ ለሚል ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ ሠርክ ለሚያጋጥመን ለምንርበተበትለት የስሜትና የእሳቦት ለጋ ህይወትም ጭምር ነዉ። ነቢይ በመቅድሙ እንደፃፈዉ ከሆነ ለጭብጥ ቅርፅን በማማረጥ አይደለም የሚገጥመዉ። ግን የአገጣጠምን ዘዬ ለመስበር፣ ህልም ዉስጥ ለመወራጨትም ሆነ ብሎ እንደተቀኘ ይመስክራል::
“... ቀልቤ እንደወደደ፣ ልቤ እንደፈቀደ እንጂ ለዚህ ይዘት፣ ለዚህ ሀሳብ ይሄን ቅርፅ ብዬ ምዳቤ ለመስጠት ጭንቅላቴን ይዤ ለማሰብ አልዳዳሁም። ... በዚህ የግጥም መድብሌ አልፎ አልፎ የባለቅኔ-ነፃነትን በመጠቀም ... ቃላቱን እንደፈተተኝ የተጠቀምኩበት ቦታ ይኖራል።
... እንደ “ዉሃ ዳር የቆመ ክራር” እና “ያላለቀ ቀሽም ግጥም የመሰለች ልጅ” የማሳሰሉት ግጥሞቼ፣ እንደዚሁ የእብደትና የጥጋብ ሊቼንሳዬን በመጠቀም የፃፍኳቸዉ ለየት ያሉ ፍሬዎቼ ናቸዉ። እብደቴን ለሚወዱና ለሚጋሩኝ ይሆኑ ዘንድ አክያቸዋለሁ። [ስዉር-ስፌት፥ መግቢያ]
ስዕል የወለደዉን ክራር፣ በግጥም አንቀልባ አሳድጐ
በጥልቅ የመለኮት ትንፋሽ፣ እፍ ሲል፣ ሙዚቃ አድርጐ
ጥበብ ነዉ ብሎ ሰጠና!
ይሄ የእብደት ነዉ የጤና? [ገፅ 150]
“ለካ ሰዓሊ ሲያብድ ገጣሚ ይሆናል” በሚለዉ ሶስትዮሽ ግጥሙ በአማርኛ ቅኔና ዝርዉ ያልተሞከረ ልዩ ገሃድዘለል እሳቦትና ምስሎች የተቀኘበት ነዉ። ሶስትዮሹ ዋናዉ ግጥም “ለካ ሰዓሊ...”፥ “አሪፍ እብደት” እና “ዉሃ ዳር የቆመ ክራር” ናቸዉ። የሚደንቀዉ ሶስተኛዉ ርዕስ፣ ለብቻው ንኡስ ግጥም ሳይሆን ከህልም እምብርት እንደሚገጥመን ዝብርቅርቅ ነገር፣ ግማሽ ስንኝ ሆኖ ሳለ ከመካከል ዋናዉን ርዕስ ለመቀናቀን እንጣጥ ብሎ ይወጣል። [ገፅ 148] ለስዕል ርዕስ ሆኖ ቃል ብቻ የነበረ ድንገት “ክራሩ እባህር ወደቀ/ መዋኘት አቃተዉና ያገር-አረፋ ደፈቀ።” እዚህ ከህልም፣ ከምናብ የፈለቁ ቅንጭብጫቢ ኢተጨባጭ ግዘፍ ነስተዉ የግላቸዉን ህይወት ፈጥረዉ ዕዉነታን ተሻሙት። ልክ የምናነበዉ የልቦለድ ገፀባህሪያት ከወረቀት ፈልሰዉ ክፍላችንን ሲያተራምሱ የማስተዋል ያክል ሆነ። ግጥም-ስዕል-ሙዚቃ፣ አንዱ ሌላዉን ወለደ። ከባህር የወደቀዉ ክራር ...
አረፋዉ በወጀቡ-ምት ተነድፎ ባዘቶ ሆኖ
ዉሃ በሙዚቃ አብሾ፣ ይኸዉ ጨርቁን ጥሎ አበደ
አገር ምድሩ አብሮ ራደ፣ ተራራም ቁልቁል ተናደ
ነቢይ የገጣሚን፣ የሰዓሊንና ሙዚቀኛን የጥበብ ነፃነትን፣ አለመገደብን ከዕዉነታ ብቻ ሳይሆን ከኢንቁ አእምሮ ስንቅ የሚሻ አባዜን ነዉ ህይወት የተነፈሰበት። “ያላለቀ ቀሽም ግጥም የመሰለች ልጅ” ግጥሙ የአራት ገፀባህርያት ተረክ ነዉ። አራተኛዉ “ሸዉራራ ድንክ ዉሻ” ናት። ተራኪዉ ከአንድ ቡና ቤት “መልኳ ጉራማይሌ” ከሆነች ሴት ፊት ለፊት ቁጭ ብሏል። በአእምሮዉ ዉስጥ ከራሱ ጋር ብቻ የሚያወራዉን ግለወግ - interior monologue - አስተናጋጁም ልጅቷም ቃል በቃል ይደግሙታል። በእርግጥም ያበደና የቀወሰ መሰል። እኩል ከገሃድና ከቅዠት ወጣ ገባ የሚሉ ግለሰቦች ናቸዉ። አነጋገሯ የሚያስጠላዉ ይመስላል፤ ግን ከእሷ አንደበት የፈለቀ ወይስ እየከጀላት የእሱ ባለመሆኗ እያስቃዠዉ ይሆን? ይህን የተበጠበጠ አእምሮ የግጥሙ ቅርፅና የስንኞች መዘበራረቅ የተናጋሪዉን ልቦና - psyche - አጉልተዉታል። ነባራዊዉ ከህዋሳቱ ላይ የሳለዉ ሳይሆን ከኢንቁ ህልማዊ ጓዳ ተከታትለዉ የሚሸሹ ምስሎች እንጂ። ግጥም በብጅት ላይ ሳለ ከቢጋሩ የፈረጠጡ ስንኞች፣ በየአቅጣጫዉ እየተንጫጩ ይደናገራሉ።
እኔም፥ ያልተጨረሰችዉን ቀሽም ግጥም ልጅ
ልታልቅ አንድ-አሙስ የቀራት
እራፊ ጠቀሳ ጠቀስኳት።
ከዚያም ያልተገረዘ ፈገግታ እያሳየኋት
እንዳላለቀ የገጠር መንገድ እየተንገዳገድኩ
አስፋልቱ ጋ ስደርስ፣ ቡችላዬን አገኘሁዋት
የዚያችን፣ ያልተጨረሰ ቀሽም ግጥም ልጅ ነገር
ለሸዉራራዋ ድንክ ዉሻዬ ነገርኳት!
እሷም “ O my God!
ምነዉ መጀመሪያዉኑ ሳትፃፍ ብትቀር !
እፀሃፊዉ አንጐል ዉስጥ፣
አርፎ መቀመጥ ማንን ገደለ ?!”
አለች:: [ገፅ 159]
ነቢይ ከሌላ የአማርኛ ገጣሚይን በበለጠ ገሃድዘለል ግጥሞችን የደፈረና ያስተዋወቀ ነዉ። እንድያዉም አንድ ግጥሙን “የማበጃ ሰዓት” [ገፅ 124+160] በእንግሊዘኛና በአማርኛ እያፈራረቀ “ጨረቅ ድምቡልቦቃ / አፄ ቤት ገባች አዉቃ”ን ያልተዳሰሰ ለጋ እሳቦት ዉስጥ ዘፍቆ የቀን ሱፍ አበባን ከሌሊት ጨረቃ ጋር አስተኝቶ “የኮከብ ቅርፅ ያላት / ትንሽ ቢራቢሮ፣ የፍቅር ተምሣሌት ትወልዳለች” ምናቡን ከዕዉነታ በላይ እንዲከንፍ ፈቅዶ ከ surrealism ዉስጥም ዉጭም ተዘረጋጋ:: ከዉስጡ፥ ግራ በሚያጋቡ ምስሎች፣ በህልም ድባብ እና በቋንቋ ዝብርቅርቅነት ሲሆን፤ ከዉጩ፥ ለረቂቅ እሳቦት፣ ነባራዊ ገጠመኝን ለማይመጥነዉ መብሰክሰክ ልባዊነት ማበጀቱ ነዉ።
ሆኖም ሰብአዊ መናወዝን፣ የሚቆረፍድና ዉብ ተመክሮን፣ ኢንቁ ህሊናዊ ትዉስብን ለመግራትና ለመጐልጐል ነብይ ቢሳካለትም በስዉር-ስፌት በቻ ሳይገታ መቀኘትና መድፈር አለበት። በሩህ ምናብን እሚያተጉና እሚያደፈርሱ፣ የገጣሚዉን ልቦና እሚጭሩት የትካዜና የግርምት ንቁና ኢንቁ ክስተቶች እንደ የማገዶ ዝምታ አድፍጠዉ ይጠብቁታል::

Published in ጥበብ
  • የኢትዮጵያ ህዝብ ለእግር ኳስ ያለው ፍቅር የሚደንቅ ነው---
  • ዘፈኑ ለሚቀጥለው የእግር ኳስ ድል እንደሚደመጥ ተስፋ አለኝ--
  • ለህዝብ መንደርደሪያ እና ቀብድ ሰጥቼ ከአስር ቀን በኋላ እሄዳለሁ---

ኑሮውን በአሜሪካ ቨርጂኒያ ያደረገው ድምፃዊ ይሁኔ በላይ፣ ለዜማ ደራሲው አበበ መለሰ የመታከሚያ ገንዘብ ማሰባሰቢያ ኮንሰርት ላይ ለመሳተፍ ባለፈው ሰሞን ነው ወደ ኢትዮጵያ የመጣው፡፡ የመጣበትን ጉዳይ ከፈፀመ በኋላ ያገኘችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው፣ ከድምፃዊው ጋር በሙያው በትምህርቱ፣ በአሜሪካ ኑሮውና በኢንቨስትመንቱ ዙሪያ ሰፊ ቃለምልልስ አድርጋለች፡፡
እንድታነቡት ተጋብዛችኋል;

 በህመም ላይ ለሚገኘው የዜማ ደራሲ አበበ መለሰ የመታከምያ ገንዘብ ለማሰባሰብ ባለፈው ቅዳሜ በላፍቶ ሞል በተዘጋጀው “ውለታ ኮንሰርት” ላይ ተሳትፈሃል፡፡ ቀደም ሲልም በአሜሪካ ከሌሎች ሙዚቀኞች ጋር ኮንሰርት እንደሰራችሁለት ሰምቻለሁ፡፡ እስቲ ጨዋታችንን በዚህ እንጀምር--- 

እስራኤል አገር ለኮንሰርት ሄጄ ነው ‹‹አቤ ታሟል›› የሚል ወሬ የሰማሁት፡፡ እኔ ካየሁት በኋላ የአቤን ጉዳይ ሌሎች አድናቂዎቹና የኢትዮጵያ አርቲስቶች እንዲሰሙና የአቅማቸውን እንዲያደርጉ ሚል እንደ ጓደኛም፣ እንደ ጋዜጠኛም አድርጎኝ --- በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ በቪዲዮ ቃለመጠይቅ አደረግንለትና በዩቲዩብ ለቀቅነው፡፡ ያኔ ነው እነ ሃይልዬ ለአቤ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ኮንሰርት ለማዘጋጀት ማሰባቸውን የነገሩኝ፡፡ የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ ለሚሹ ወገኖች የባንክ አካውንት ከፍተው ስለነበረም የአካውንቱን ቁጥር ከቃለምልልሱ ጋር አካተትኩት፡፡ ሌሎች ሚዲያዎችም መረጃውን እየወሰዱ ማስተላለፍ ጀመሩ፡፡
ከዛ በኋላ አሜሪካ ያሉትን አርቲስቶች አቀናጅተን ትንሽ ገንዘብ ማሰባሰብ ነበረብን፡፡ እዛ ያለው የስራ ጫናና ኑሮ ደግሞ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ በአሜሪካ ከራስ አልፎ ጊዜን ለሰው መስጠት ትንሽ ይከብዳል፡፡ ሆኖም እንደምንም ብዬ አርቲስቶች በማሰባሰብ ኮሚቴ አቋቋምንና ተወያይተን ‹‹መዓዛ ሬስቶራንት›› ውስጥ የሙዚቃ ዝግጅት ለማቅረብ ተስማማን፡፡ አንዳንድ ጉዳዮች ሲኖሩን እዚያ ሬስቶራንት ውስጥ ነው የምንሰራው፡የሬስቶራንቱ ባለቤት እንደዚህ አይነት ጉዳዮች ሲኖሩ ትተባበራለች፡፡
በእዚህ ኮንሰርት ላይ የተሳተፉት እነማን ነበሩ? ምን ያህል ገቢስ ተገኘ?
የመግቢያ ዋጋው 25 ዶላር ነበር፡፡ እሱን ለመርዳት ብለው ትኬት ቆርጠው የገቡም በጥሪው ገንዘብ የሰጡም አሉ፡፡ አበበን ለመርዳት የተቻለውን ያህል ተረባርበናል፡፡ በዝግጅቱ አርቲስት መሃሙድ አህመድ ነበረበት፡፡ ሌሎችም በርካታ ሙዚቀኞች ተሳትፈዋል፡፡ ከኮሚቴው አባላት መካከል ገጣሚ አለምጸሃይ ወዳጆ፣ ጋዜጠኛ አበበ ፈለቀ፣ ፀሃይ ካሳ፣ ደሳለኝ መልኩ፣ ዳምጠው(ተወዛዋዥ) ወደ አስር ገደማ ይሆናሉ፡፡ ከቦታው ጥበት አንፃር ብዙ ታዳሚዎች አልነበሩም፡፡ ኮንሰርቱን ትልቅ አዳራሽ ውስጥ ብናደርገው ኖሮ …ችግሩ ግን አሜሪካ ሰፊ አዳራሽ ለመከራይት ክፍያው ብዙ ነው፡፡ እንደውም ገቢውን በሙሉ እንዳይወስደው በመፍራት ነው በዚያ መልኩ እንዲሆን የመረጥነው፡፡ ከኮንሰርቱ 12 ሺ 500 ዶላር (212 ሺ 500 ብር ያህል) ተገኝቷል። የገንዘብ ማሰባሰቢያ ኮንሰርቱ አሁንም ይቀጥላል። አበበ ህክምናውን ለማጠናቀቅ የሚያስችል ገንዘብ እስኪያገኝ ድረስ ህይወቱን ለመታደግ ጥረታችንን እንቀጥላለን፡፡ አርቲስቶች በዚህ ተስማምተን ነው የተለያየነው፡፡
ከሳምንት በፊት ደግሞ ከዚሁ አርቲስት ገንዘብ ማሰባሰቢያ በተዘጋጀው ‹‹ውለታ ኮንሰርት›› ላይ ለመሳተፍ ወደ ኢትዮጵያ መጣህ–
አዎ ስመጣ ሙዚቀኞች ጥናት ላይ ነበሩ። ፖስተር ሁሉ ተዘጋጅቷል፡፡ እኔ እንደምኖር ስላልታወቀ ለህዝብ አልተገለፀም ነበር፡፡ ሆኖም በሰዓቱ ደርሼበታለሁ፤ እናም ሙዚቀኞች የ‹‹ዘገሊላ ዕለት›› የሚለውን ሙዚቃዬን አጠኑልኝና ደስ ብሎኝ ኮንሰርቱ ላይ ተጫወትኩ፡፡
ከአሁኑ ኮንሰርት ውጪ ኢትዮጵያ ውስጥ ኮንሰርት ሰርተህ አታውቅም--- ለምንድን ነው?
በአሁኑ ኮንሰርት እንደ ሰርፕራይዝ ነው የቀረብኩት፡፡ ህዝቡ ናፍቆኝ ስለነበረ በዚያች አጭር ጊዜ ውስጥ ከእስክስታውና ከዘፈኑ ጋር ተዳምሮ ደስታዬን እጥፍ ድርብ አድርጎልኛል፡፡ በእውነቱ በጣም ነው የተደነቅሁት---እንዴት ደስ አለኝ መሰለሽ---የኢትዮጵያ ህዝብ ሰው ማዳን የሚችል..ፍቅር የሆነ… አንቺ ምን ዓይነት ህዝብ ነው፡፡ በጣም ነው የተደሰትኩ---.ለሙዚቃ ያለው ፍቅር..እንባዬ ሁሉ ነው የመጣው..ቦታው ጢም ብሎ ሞልቶ ነበር፡፡ ታዳሚው ይጫወታል --- ይጨፍራል-- ይደሰታል…ይሄ እንግዲህ በአዲስ አበባ የመጀመሪያዬ ኮንሰርት ነው፡፡ መቼም ያየሁት ድባብ ልዩ ነበር፡፡ ህዝቡ ከእኔ ጋር በጣም ሲዘል፣ ሲጨፍር ነው ያመሸው፡፡ አይተሽው አይደል--
አዎ አይቼዋለሁ፡፡ እኔ የምለው-- አበበ መለሰ ለአንተ ዜማ ሰጥቶሃል እንዴ?
አልሰጠኝም፡፡ ግን አበበ ይሄ ሲያንሰው ነው። ከዚህ በላይ ሊደረግለትና፣ ብዙ መስዋዕትነት ሊከፈልለት የሚገባው አርቲስት ነው፡፡..
እንግዲህ ‹‹ውለታ ኮንሰርት›› አስፈንድቆኛል ብለሃል፡፡ ወደፊትስ እዚህ መጥተህ ኮንሰርት ለማቅረብ አላሰብክም?
ለአዲስ አመት አዲሱን ሙሉ አልበሜን ለማድረስ ዝግጅቴን አጠናቅቄአለሁ፡፡ በአገኘሁት አጋጣሚ ቀን ማታ ሳልል ግጥምና ዜማዎችን እያሰባሰብኩ ነው፡፡ በነገርሽ ላይ ባለፈው እሁድ ኢትዮጵያ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ያደረገችውን ጨዋታ ተመልክቼ በጣም ነበር ደስ ያለኝ፡፡ ከድሉ በኋላ ስቱዲዮ ገብቼ ከአዲሱ ስራዬ ውስጥ ለአንድ ጉዳይ ያዘጋጀሁት ዘፈን ነበር --- ከእርሱ ላይ ቆረጥ ቆረጥ አድርጌ ለኢትዮጵያ ህዝብ ‹‹የእንኳን ደስ ያላችሁ›› ዜማ ሰርቼአለሁ፡፡
እስኪ ከዘፈኑ ግጥም ቀንጨብ አድርገህ ንገረን--
‹‹ዛሬ ነው ዛሬ ፋሲካ ነው ደስታ ነው ዛሬ
እንኳን ደስ አለሽ ኢትዮጵያ ሃገሬ››
የሚልና ተጫዋቾቹን የሚያወድስ ነው፡፡ ይሄን ዜማ ሌሊቱን ስንሰራ አድረን ነው የጨረስነው፡፡ የሙዚቃ ባለሞያዎች እንቅልፍ አጥተው ከእኔ ጋር አድረዋል፡፡ ግጥሙ የፀጋዬ ደቦጭ ሲሆን ዜማው የእኔ ነው፡፡ እነ አበበ ብርሃኔ፣ ሄኖክና ሌሎች ጓደኞቼ አብረውኝ ነበሩ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ለኳስ ያለው ፍቅር የሚደንቅ ነው፡፡ በባህላችን ደግሞ ድል ሲገኝ ‹‹እንኳን ደስ ያላችሁ ›› የመባባል ነገር ስላለ ነው ያንን ሙዚቃ የሰራሁት፡፡ እና ሌሊት ስንሰራ አድረን..ጠዋት ሲዲውን ለሚዲያ ልንሰጥ ስንል ግን ሌላ ነገር ተፈጠረ፡፡ አስደንጋጭ ዜና ሰማን። የእኛም ዘፈን ለጆሮ ለመብቃት ሳይታደል ቀረ፡፡ ዞሮ ዞሮ ውጤቱ ቡድናችን ለወደፊቱ ያለውን ተስፋ ጠቋሚ ነው፡፡ በተጨዋቾቻችንም እንኮራለን፡፡ ዘፈኑ ለሚቀጥለው ተመሳሳይ ድል እንደሚደመጥ ተስፋ አለኝ፡፡
አንድ ጊዜ ስትናገር--- ዘፈኖቼ ሳላስበው ከባህላዊ ወደ ዘመናዊነት እየወሰዱኝ ነው ብለህ ነበር፡፡ በአዲሱ ስራህስ?
በአዲሱ አልበም ባህላዊም ዘመናዊም ዘፈኖች ይካተታሉ፡፡ ‹‹የዘገሊላ እለት››፣ ‹‹አውማ››፣ ‹‹ዘንገና››--ሁሉም ነገሮች አሉበት፡፡ አቅሜ የፈቀደውን ያህል ጣፋጭ ዜማዎች ለህዝብ ለማድረስ እየሰራሁ ነው፡፡ ባህላዊ ነገሩ ቅድሚያ ተሰጥቶት ነው እየተሰራ ያለው.. አድማጮቼ በአዲሱ ስራዬ ትደሰታላችሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ስራዎቹ ባህላዊም ዘመናዊም ናቸው። ለአዲስ ዓመት የሚወጣ ሙሉ ካሴትና በቅርቡ የሚለቀቅ ነጠላ ዜማ አለኝ፡፡ መንደርደሪያ እና ቀብድ ሰጥቼ ከአስር ቀን በኋላ እሄዳለሁ፡፡
አባትህም ድምፃዊ ነበሩ ይባላል---እንደውም የአንድ ዘፈን ግጥም እንደሰጡህ ሰምቻለሁ---
አባቴ ከገጠር እየተመላለሰ ነበር የሚያየን፡፡ አባቴንም ሆነ ትልልቅ ሰዎች ወደ እኛ ቤት ሲመጡ መጠየቅ ደስ ይለኝ ነበር፡፡ አባቴንም እጠይቀው ነበር፡፡ ‹‹ለፍቅር…ለወደዳችኋት ልጅ፣ ለፋሲካም ሆነ ለገና በዓል ምን እያላችሁ ነው የምትዘፍኑት›› ብዬ ስጠይቀው፤
‹‹የዛሬን እኔ አለሁ አሳድርሻለሁ፣
ደግሞ ለነገው ይፈለጋል ሠው›› ነው የምንላት ብሎ ነገረኝ፡፡ ይሄንንም ‹‹እህና ናና ሆይና›› በሚለው ዘፈኔ ላይ ተጫውቼዋለሁ፡፡ በእኔ ሙዚቀኝነት ውስጥ የአባቴ ድርሻ ጉልህ ሥፍራ አለው። በአጠቃላይ የገጠሩ ህብረተሰብ አካል ነኝ። መሆን የምፈልገው፤ ይዤ የተነሳሁትም የአገሬን ባህል፣ቋንቋውን ማሳወቅ፣ ማስከበር ነው፡፡ ባህሌን ማሳወቅ የእኔ ግዴታ፣ ውዴታም ነው፡፡
እንደ ‹‹እህና ናና ሆይ እና››፣ ‹‹ሎጋው ሽቦ››፣ ‹‹የማይ ውሃ›› የመሳሰሉ የህዝብ ዜማዎች ትርጉማቸው ጠጠር ይላል የሚሉ ወገኖች አሉ----
በቃ እኮ ከህዝብ የሚፈልቅ ስሜት ነው፡፡ የፈጠራ፣ የጥበብ ሰው እኮ ነው ባላገር፡፡ የገጠሩ አካባቢ ሰው ሁሉም ዘፋኝ፣ አቀንቃኝ፣ ገጣሚ ነው፡፡ ቋንቋው የበሰለና ጥበብ የታከለበት ነው። በቃ ቅኔ ነው--- የህዝብ ህብረ ቀለም ያለው ቅኔ፣ የሚጣፍጥ--ከውስጥ ጥልቅ የሚል ቋንቋውና ፍሰቱ የሚያስደንቅሽ…ድንቅ ህዝብ፣ ድንቅ የባህልና የፈጠራ ባለቤት ነው ባላገር.. እኔ ይሄ ነኝ---የዚህ ህዝብ አካል፡፡
የአሜሪካ ኑሮህ እንዴት ነው?
አሜሪካ ስኖር ጎደለኝ የምለው ነገር የለም፤ እግዚአብሄር ይመስገን ሁሉ ሙሉ ነው፡፡ እኔ ደስ የሚለኝ በሃሳብ ወደ ኋላ ተመልሼ፣ የልጅነት ጊዜዬን፣ አገር ቤትን በትዝታ ስቃኝ ነው፡፡ በተለይ…ፍኖተ ሠላምን-- ያደኩበትን ሠፈር፣ጓደኞቼን አይቼ ስመለስ ስራዬን እንዴት እንደምሰራ አታውቂም! በተረፈ ግን..ብዙ ነገሮች ለእኔ ድግግሞሽ ናቸው። ልጆቼን ገጠር የአባቴ አገር ይዣቸው ሄጄ ደበሎ አልብሻቸዋለሁ፡፡ ሴትዋን ልጄን ባለገመዱን ቀሚስና መቀነት አልብሻታለሁ፡፡ ባህላቸውን አውቀው እንዲያድጉ ከከብቶች ጋር ፎቶ አንስቻቸዋለሁ፡፡ እንደውም ‹‹እምዬ ኢትዮጵያ አገረ ገነት›› የሚለው ዘፈኔ ቪድዮ ክሊፕ መፅሐፍ ቅዱስ እያነበብን ነው የሚጀምረው፡፡ ልጆቼ ይህን እንዲያገኙ፣ እንዲያውቁ፣ እንዲኮሩበት ስለምሻ ሁሌም አስተምራቸዋለሁ፡፡. ደበሎ ለብሰን አድገን በአሜሪካ የምንወልዳቸው ልጆች ባህላችንንና እኛን አያውቁንም፡፡ መሠረታችንን አመጣጣችንን አያውቁም… ብናግዛቸው መልካም ነው፡፡
ትምህርት እንደጨረስክ ነው ”ጊሽ ዓባይ” ኪነት ቡድንን የተቀላቀልከው?
ከዛ በፊት ለአንድ ወር በመሠረተ ትምህርት ዘመቻ ላይ ተሳትፌአለሁ፡፡ ባከል ገብርኤል ላይ ነበር የዘመትኩት፡፡ ገበሬው ደስ ይለው ነበር። ለአስተማሪ ትልቅ ክብር ስላለው ቤቱ አግብቶ ያበላል ያጠጣል… እንዴት ሰው ያከብራሉ መሰለሽ፡፡ በጣም ፍቅር ነው የገጠሩ ህብረተሰብ፡፡
ወደ “ጊሽ ዓባይ” እንግባ…
በ1979 ዓ.ም ነበር፡፡ ‹‹አንቱየዋ እነሱ እኮ ልጆች ናቸው ይጫወቱ በጊዜያቸው›› የሚለውን የሙዚቃ ፕሮግራም እኔ ነበርኩ ይዠው የሄድኩት፡፡ ፈጠራው የእኔ ነው፤ እኔ ነኝ የትርኢቱን ንድፍ (ስኬለተን የሰራሁት) ይሄ አለኝ ብዬ ስሰጣቸው የ “ጊሽ ዓባይ” ትርዒት ኃላፊ እሱባለው ጫኔ ..ሰማኸኝ በለው/አባት ፣ ሀብቱ/እረኛ፤ አለምወርቅ አስፋው/እናት፣ ብዙአየሁ ጎበዜ/ልጅ ሆኑና--ወዲያው ተቀነባበረ። እዛ ከደረሰ በኋላ እየተቀየረ መጣ..ሁሉም ሰው የራሱን ፈጠራ ይጨምራል..አንዱን ቀን የሰራነው ሌላ ቀን ሌላ ይጨመርበታል..እያደገ መጣ..ያን ከሰራን በኋላ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጠሩን፡፡ እድገቴ ፈጣን ነበር፡፡ በ1981 ዓ.ም ካሴት አወጣሁ..‹‹የአገሬ ልጅ ባለጋሜ ትውልደ ጎጃሜ›› የሚለውን፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ አዲስ አበባ ስትመጣ ምን ዓይነት ስሜት ፈጠረብህ?
ከክፍለ ሃገር ለሚመጣ ሰው ደስ የምትል ከተማ ናት፡፡ መኪና ውስጥ ሆኜ--አዲስ አበባ ደረስን እስኪባል ድረስ አቀነቅን ነበር፡፡ የመጀመሪያው የህብረት ጉዞ ነበር፡፡ በየቦታው አብረን ነበር የምንቀሳቀሰው፡፡ ሁለተኛ ካሴት ለማሳተም ስመጣ ብቻዬን ስለመጣሁ--ትንሽ አደናግሮኝ ነበር፡፡ ከጎጃም የሚመጣ ሰው ማረፊያው ጎጃም በረንዳ ነው፡፡ ጎጃም በረንዳ ሆኜ በፊት ስመጣ ለተዋወቅኋቸው ጓደኞቼ ደወልኩላቸው፡፡ ማሲንቆ ተጫዋች አበበ ፈቃደ የሚባል አሁን ካናዳ ነው … ሁለት ቀን ከሆነኝ በኋላ ደወልኩለትና መጣ፡፡
‹‹ምን ሆነህ መጣህ›› አለኝ፡፡
‹‹ካሴት ላወጣ›› አልኩት፡፡
‹‹እና እዚህ ሆነህ ነው የምታወጣ›› አለኝ፡፡
የአዲስ አበባን የኑሮ ውድነት ስለሚያውቅ ነው እንደዚህ ያለኝ፡፡ ከዛ ይዞኝ ሄደ፡፡
የምሽት ክበብ ውስጥ አስቀጠረህ?
ጓደኛዬ ማታ ማታ ክለብ ውስጥ ይሰራ ነበር… እሱን ተከትዬ እሄድኩ ሲጫወት እሰማዋለሁ። ነገሮችን አጤናለሁ፡፡ ካሴት ካወጣሁ በኋላ ነው ካራማራ የተባለ ናይት ክለብ ውስጥ መስራት የጀመርኩት፡፡ ለአንድ ዓመት ከሰራሁ በኋላ አይቤክስ ሲከፈት፣ ሙዚቀኞችን አሰባስቤ ኮንትራት ወስጄ እየሰራሁ ሳለሁ ነው ወደ አሜሪካ የመሄድ እድል የገጠመኝ፡፡
አሜሪካ ከገባህ በኋላ በሙዚቃው ብቻ ሳይሆን በንግዱም ተሳክቶልሃል ይባላል…
አሜሪካ ሰፊ እድል አጋጥሞኛል፡፡ እንደሄድኩ ያላሰብኩት ጥሩ ፍቅር ገጠመኝ - ከአሁኗ ባለቤቴ ጋር። የባለቤቴ ራዕይና መልካም አቀራረብ ገዛኝና ጋብቻ መሰረትን፡፡ በትዳሬና በልጆቼ ደስተኛ ስለሆንኩ--በምሄድበት ቦታ ሁሉ ይቀናኛል። የመጀመሪያ ልጄ ፍቅር ይሁኔ ይባላል፡፡ ሴትዋ ሰላም ይሁኔ ትባላለች፡፡ ባለቤቴ ደግሞ የሺእመቤት ተስፋዬ፡፡ በአሜሪካ የሺእመቤት በላይ ነው የምትባለው፡፡ “ዘ በላይ ፋሚሊ” ተብለን ነው የምንጠራው፡፡ ባለቤቴ በቢዝነስ ነው የተመረቀችው---የእኔ ስራ እየዞሩ ኮንሰርት ማቅረብ ነው፡፡ በኋላ “ኢትዮጵያን የሎው ፔጅስ” የሚባል የመረጃ መጽሐፍ ማሳተም ጀመርን፡፡ እንደ ቢቢስ እና ሲኤንኤን ያሉ አለማቀፍ ሚዲያዎች ስለመጽሐፉ ብዙ ዘግበዋል፡፡ በዋሺንግተን ዲሲ የሎው ፔጅ በጣም የታወቀ ካምፓኒ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ኮሙኒቲ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ፈጥሮልናል - ጥሩ መረጃ ነው የምንሰጣቸው፡፡ አሜሪካን አገር የሎው ፔጅ የሚባል ትልቅ የመረጃ መስጫ መፅሃፍ አለ - አሜሪካኖች በስፋት የሚጠቀሙበት፡፡ ባለቤቴ ያንን አይታ ነው ለምን ለኢትዮጵያ ተመሳሳይ ነገር አንጀምርም ብላ የጀመርነው፡፡ በየዓመቱ የሚወጣ ነው…በዚህ ስራ ላይ ለአስራ ዘጠኝ ዓመት ሰርተናል፡፡
በካምፓኒያችሁ አማካኝነት ከአሜሪካውያን ታዋቂ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ሙዚቀኞችና ተዋንያኖች ጋር ግንኙነት መፍጠር እንደቻላችሁ ሰምቼአለሁ--
አዎ--- ሂላሪ ክሊንተን፣ ጆን ማኬን፣ ዴንዝል ዋሽንግተን፣ ኤሪክ ቤኔ፣ ዳጊ ፍሬሽ/ራፐር/…እንዲሁም ከበርካታ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ሙዚቀኞችና ተዋንያኖች ጋር በሰፊው እንገናኛለን..በቅርቡ እንደውም አንዲት ኢትዮጵያዊት ከጥቁር አሜሪካዊ ጋር ተጋብታ እኔ ነበርኩ የሰርጉን ሙዚቃ የሰራሁላት፡፡
በፌስ ቡክ ፔጅህ ላይ የምርቃት ፎቶ አይቻለሁ። በምንድነው የተመረቅኸው?
ላለፉት ሁለት ዓመታት ትምህርት ቤት ነበርኩ፡፡ በኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ ነው የተመረቅሁት፡፡ የኮምፒዩተር ጤንነትን በተመለከተ፣ ኮምፒዩተርን ቢዩልድ ማድረግ--ኔትዎርክ፣ ኢንተርኔት ሴኪዩሪቲ ተምሬአለሁ፡፡ ከአራት ወር በኋላ ደግሞ በ“አርት ኤንድ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ” እመረቃለሁ፡፡ ወደፊትም መማሬን እቀጥላለሁ፡፡
በአገር ውስጥስ ኢንቨስት ለማድረግ አላሰብክም?
ብዙ ሃሳቦች አለኝ፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት መጥቼ ፍኖተ ሠላምን ሳያት እየተለወጠች ነበር፡፡ አዳዲስ ግንባታዎች አሉ…በፍኖተ ሠላም ትልቅ ባዛር የተካሄደ ጊዜ “አንተም ልጃችን ነህ፤ የበኩልህን አስተዋፅዖ አድርግ” ተባልኩ፡፡ አፋጣኝ ምላሽ ነበር የሰጠሁት፡፡ ሁሉን ነገር ትቼ በሶስት ቀን ውስጥ ወደ አዲስ አበባ መጣሁ፡፡ ከዛም ወደ ፍኖተ ሠላም ሄድኩ፡፡ እንደ ጠዋት አዲስ አበባ ገብቼ ወዲያው በመኪና ተሳፍሬ ፍኖተ ሠላም ከምሽቱ አራት ሰዓት ነው የገባሁት፡፡
ህዝቡ፣ ከችኳንታ እስከ አውቶብስ፣ ባጃጁ ሳይቀር… ከፍኖተ ሠላም ተነስቶ ጅጋ የምትባል 12 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ቦታ ድረስ መጥቶ እንደ ሙሽራ አጅቦ፣ እየፎከረ እየሸለለ አጅቦ አስገባኝ---ይህን ሳይ በጣም ነው ያለቀስኩት፡፡ ስደርስ የባዛሩ መዝጊያ ደርሶ ነበር፤ ሁለት ቀን ኮንሰርት ሰርቼ ተመለስኩ፡፡ ምን ያህል ገቢ እንደተገኘ ባላውቅም ገቢው ለከተማዋ የሚውል ነበር፡፡ ኢንቨስትመንቱን በተመለከተ ግን የጀመርኩት ነገር ጥሩ ደረጃ ሲደርስ እነግርሻለሁ፡፡
በባዛሩ ኮንሰርት ላይ አንተን ይተካል ተብሎ የሚጠበቀው የአካባቢህ ልጅ ሰለሞን ደምሴ “ነይማ ላሳይስ ነይማ ጎጃም ፍኖተ ሠላም” እያለ ሲያቀነቅን የእጅ ሰዓትህን አውልቀህ ሸልመኸዋል ይባላል--
የሚገርም ድምፃዊ ነው፡፡ በጣም የሚያድግ ልጅ ነው፡፡ እኛም ድሮ እንደዚህ የሚያበረታታን ስናገኝ ደስ ይለን ነበር፡፡ ለዚህ ነው ሲጫወት ሳየው ስላስደሰተኝ የእጄን ሰዓት ፈትቼ የሸለምኩት፡፡
ቀረ የምትለው ካለ…
እግዚአብሄር ያክብራችሁ፡፡ ጎተራውን ሙሉ…አገሩን ጥጋብ ያድርግላችሁ..አይለየን..አለማችሁን ያሳያችሁ…ፍቅር፣ ሰላም፣ ደስታ ከእናተ ጋር ይሁን!

Published in ጥበብ

                 የማደግ መብታቸው ተከብሮላቸዋል። መንገዶቹ፣ ቤቶቹ፣ የቴሌኮሙኒኬሽን አማራጮቹ፣ የገቢ እና የወጪ ልኮቹ፣ ግድቦቹ … የማደግ መብታቸው ተከብሮላቸዋል፡፡ ተይዘው ነበር፣ ደንዝዘው ነበር፣ ሞተው ነበር…የማደግ መብታቸው በሰው አማካኝነት ተከብሮላቸዋል፡፡ ከመያዝ፣ ከመደንዘዝ፣ ከመሞትም በኋላ አፈር ልሶ መነሳት ይቻላል፡፡ ለእነሱ መብታቸውን ያስከበረላቸው ያ የፈረደበት ሰውስ? የማደግ መብቱ ተከብሮለታል?... በእነዚህ በስልጡን ቤቶች ውስጥ ገብቶ እንዲኖር የታሰበው ሰው በሰለጠነ መንገድ የሚያስብ መሆን አለበት፡፡ በታደሰ ቋንቋ መናገር አለበት፡፡ ከተነሳበት እስከሚደርስበት ለመጓዝ ፈጣን መኪና ገዝቶ ፈጣን መንገድ አጥቶ ተጨነቀ፤ ጭንቀቱ መፍትሔ እያገኘ ነው፡፡ ፈጣኑን መኪና፣ በፈጣኑ መንገድ ላይ የሚያሽከረክረው የህዳሴው ዘመን ሰው፤ ከመኪናው ፍጥነት እኩል ማሰብ … ከጥያቄው ወደ መልሱ መድረስ ካልቻለ…ለአኗኗር ዘይቤው የማደግ መብትን ሰጥቶ ለራሱ ግን የነፈገ ሞኝ ሆኗል፡፡

ተሸውዷል! (ምናልባት የትራፊክ አደጋዎቹ የበዙት በዚህ ምክንያት ይሆን? የመኪናውንና መንገዱን ያህል ያልፈጠነ፣ ያልሰለጠነ፣ ያልታደሰ አሽከርካሪ እያሽከረከራቸው ይሆን?...መልሱ፡- እንዴታ! የሚሆን ይመስለኛል፡፡ ከመሰለኝ ደግሞ ነው!) በጎጆ ቤት ኑሮውን የሚገፋ ጐጆ ቤትን መሳይ (የግርግም) አስተሳሰብ ያለው ሰው መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ (ካጠያየቀም፤ ተጠያያቂዎቹ ከጥያቄው ክብደት ጋር የማይመጥኑ ናቸው፡፡) በዋሻ ውስጥ ይኖር የነበረው የኒያንደርታይል ዝግመት ዘመን ሰው፣ ወደ ጐጆ ቤት ከገባ…እንደ መሬት አራሾቹ ገበሬዎች ራሱን አሳድጐ መኖር አለበት፡፡ መንጋት እና መምሸትን ብቻ ሳይሆን ወቅቶችንም መቁጠር መጀመር ይኖርበታል፡፡ ከቤቱ እድገት ጋር ተመሳስሎ መሰልጠን ግዴታው ነው፡፡ ካልሆነ ጐጆው ውስጥ የገባው የዋሻ አውሬነቱን ይዞ ይሆናል፡፡

ፎቅ ቤት ውስጥ ለመኖር የተዘጋጀ ትውልድን ወደ ጐጆ ወይንም ወደ ዋሻ ማስገባት አይቻልም። ኑሮው እና ነዋሪው አይመጣጠኑም፡፡ በፎቅ ቤት ቋንቋ ጐጆ ውስጥ ማውራት የሳር ቤቱ ላይ እሳት ለመለኮስ ነው፡፡ ለኩሶ ቢያቃጥለው ጥሩ ነው፤ የሚመጥነውን ቤት በፋንታው ይሰራል፡፡ በዚህ እይታ የእድገትን ነፃነት እንደ አርዕስት አንስተን መወያየት እንችላለን፡፡ የከተማ መልክ ያወጣ ሰው ፊት፣ ከተማውን መስሎ መኖር መቻሉን የፊቱ ስልጡንነት አመልካች ነው፡፡ ከተማ ውስጥ ኩታ እና ተነፋነፍ አድርጐ የሚዞር ሰው እየኖረ ያለው በድራማ እስክሪፕት ውስጥ ነው፡፡ የድራማ እስክሪፕቱም “ትራጃይክ ኮሜዲ” ተብሎ ይጠራል፡፡ የፈረንሳዩ ፈላስፋ ዴካርት እና በጊዜው የነበሩ ተከታዮቹ (Such as cordemey) አንድ ፍጡር መስተሐልይ እንዳለው ማረጋገጥ የሚቻለው (በአይን ከሚታየው የራስ ቅሉ ባሻገር) የቋንቋ አጠቃቀሙ ላይ ነው፡፡ አዳዲስ ሀሳብን እና ሐሊዮቶችን የሚገልጽ እና ገለፃውን መሸከም የሚችል ቋንቋ ሲኖረው ነው፤ ይላሉ፡፡ ከዴካርት እና ካርቲዣኖቹ ጋር ካልተስማማን ጃጄ ሩሶ ይጨምርበታል፡፡

“የሰው ልጅ የማንነቱ ብቸኛ መለያ ራሱን ማሻሻል እና ወደ ፍፁምነት ለመድረስ መሞከርን መቻሉ ነው” ይላል፡፡ “Faculty of self – perfection which with the aid of circumstance, successively develops all the others, and resides among us as much in the species as in the individual” ራስን እና የሰው ልጆችን ወደ ፍፁማዊነት መምራት የባህላዊ ህዳሴን በማካሄድ የሚለው ሃሳብ በዴካርት አልተጠቀሰም፡፡ የተጠቀሰው በ “ሩሶ” ነው፡፡ የሁለቱን ፈላስፎች እይታ ጨርፌ ማቅረቤ ማረጋገጫ ይሆነኛል ብዬ አይደለም፡፡ ማጣቀሻ ወይንም መንደርደሪያ እንጂ ለሌላ አይሆኑም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ፈላስፎችም ዘመናዊ ፍልስፍና ከደረሰበት ስልጣኔ አንፃር እንደ ጐጆ ቤት የሚታዩ ናቸው፡፡ ነገር ግን ከእነዚህ ጐጆ ቤቶች ተነስተው ነው ምዕራባዊያኑ ወደ ሰማይ ጠቀስ የአስተሳሰብ ህንፃዎቻቸው የተሸጋገሩት፡፡ እኛም እስቲ እንደነሱ ለሙከራ ያህል እናስብና ወደ ዘመናዊ ስልጣኔያችን ይዘን የምንገባቸውን ቋንቋዎች እንፈብርክ፡፡ ኃይል ማመንጫዎቻችን የሚያመነጩትን ሜጋ ዋት የሚመጣጠኑ ሐሳቦችን የሚያመነጩ ቋንቋዎችን፡፡ ግን እንዴት ነው የምፈበርከው? … ነፃነት ከሌለ። አዳዲሶቹ መንገዶች እና ፎቆች ከዛጉ ቆርቆሮ ቤትነታቸው እንዲያድጉ የተደረጉት የማደግ ነፃነት ተሰጥቷቸው ነው፡፡ ቋንቋ እንዲያድግም ነፃነት ያስፈልገዋል፡፡

ቋንቋ ማለት ሀሳብ ነው፡፡ የሐሳብ እድገት በነፃነት ብቻ ይመጣል፡፡ ፎቆቹ እንዲያድጉ፣ ካለማደግ ባርነት ሰንሰለታቸውን እንደ ጤዛ በትኖ የለቀቃቸው አካል፤ ቋንቋንም እንዲያድግ መፍቀድ አለበት፡፡ በቋንቋ፣ በማሰብ፣ ራስን በመግለጽ፣ በመወያየት፣ በመቃወምና በመስማማት…ውስጥ ነፃነቱን ይቀዳጃል፡፡ ቋንቋ ነፃ ከተለቀቀ ማደጉ አይቀርም፡፡ ማደጉ የአእምሮ ማደግንም ጠቅልሎ ነው፡፡ የሚያድገው ደግሞ ፎቆቹ ወዳደጉበት አቅጣጫ መሆኑ አያጠራጥረኝም፡፡ ከተማው የማደግ ነፃነቱ ሲከበርለት ፎቅ ሆኖ ከበቀለ…የከተማ ነዋሪው አስተሳሰብ የማደግ ነፃነት (ራሱን በነፃነት በመግለጽ) ረገድ ክብር ሲሰጠው ወደ ጐጆ ቤት ወይንም ወደ ጫካ(ፍሬ ለቀማ) ኑሮ የሚገባ አይመስለኝም፡፡ በዋሻ ውስጥ አውሬ ሆኖም አይጮህም፡፡ ወደ ኋላ የሚያድግ አይመስለኝም፤ ካደገ ግን ከፍተኛ አይ - አዎ (Paradox) ነው የሚሆነው፡፡ አንድም፡- ፎቅ ቤት፤ እና መንገድ፤ እንደዚሁም ግድብ… ስልጣኔ አይደሉም፤ ወይንም ስልጣኔ ለደሀ ህዝብ አያስፈልግም ማለት ነው፡፡ ደሀ ምን ማለት እንደሆነ ድህነትን ብንጠይቀው ይነግረናል፡፡

እድገት ስልጣኔ ነው፡፡ እድገት ያስፈልጋል ማለት የሰው ልጅ ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ የሰው ልጅ ታሪክ የእድገት እና የስልጣኔ እንደመሆኑ መጠን፡፡ ስለዚህ የፎቅ መብቀል ክፉ ነገር ሊሆን አይችልም፡፡ ክፉ የሚሆነው ወደ ፎቅ ቤቱ ይዘን የምንገባው የድሮ ኋላቀርነታችንን በጥንቱ የአስተሳሰብ አንቀልባችን አዝለን ከሆነ ነው፡፡ የአስተሳሰብ ስልጣኔ በእውቀት ብቻ ይጨበጣል፡፡ እውቀት፤ ….ቃላትን ወደ ቋንቋ፣ ቋንቋን ወደ ሃሳብ፣ ሃሳብን ወደ ሐሊዮት፣ ሐሊዮትን ወደ ሙከራና ተግባር በመቀየር የሚገኝ ነው፡፡ በድሮ እውቀት የምንቀረው የድሮው ማንነታችን ውስጥ ነው፡፡ አዲስ እውቀት ላይ ደርሰን የሰራነው ህዳሴ እንዲስማማን … ሃሳባችንን ከስልጣኔው ፍጥነት ልክ ማስማማት አለብን፡፡ ቁሳቁሶች እንዲሻሻሉ በተሰጣቸው ነፃነት አንፃር የማሰብ መብትም ነፃ ቢሆኑልን ምኞቴ ነው፡፡ ለ “ሁሉም በጄ ሁሉም በደጄ” ማመልከቻ አቀርባለሁ፡፡

Published in ጥበብ
Saturday, 22 June 2013 11:56

አፈር አፈር ብላ

አፈር-አፈር ይብላ፤
ለእግዜር እግዜር ይየው፤
እንዴት ነው የሣት ፍም በአፈር የሚቆየው
እንዴት ነው ነበልባል - በእሣት የሚጋየው
ኮከብ እንዴት ብሎ - ለአፈር ይገዛል?
እንዴት ፀሐይ - ወርዶ መሬት ይያዛል?
አፈር አፈር ብላ - አጥንቷ ይንሣህ
ሥጋዋ ረፍት ይንሣህ
ሀሣብዋ ይነቅንቅህ!
መልክ አይሁንህ ደምዋ
ዓመዱን ይርጭብህ - ለዛህን ይንጠቀው
ሠላምህን ይውሰድ - ልብህን ይሥረቀው
የዲከንስን ገላ - ሞቆህ የታቀፍከው
አበባ ሀሣብዋ ደልቶህ - ያረገፍከው
አፈር-አፈር ብላ!
ዋይታ ይሁን ውስጥህ - ነጋሪቷን አሥረህ
ቃልዋን ሥላፈንከው፣
“ኡ!” ያሠኝህ ዘመን - ያ ቃል ውበቷ
አንጀትክን ያሣርረው
አፈር አፈር ብላ - ውቅያኖስ ባህሩ
ሬሣህን ይቅበረው !
እኛ እንዘምራለን - ለኤሚል ዲክንሰን
ከነፍሳችን ጋራ አብራ ለምትበርረው !

Published in የግጥም ጥግ
Saturday, 22 June 2013 11:47

እምቢኝ!

በእኔና በእነሱ መካከል ያለው ድልድይ ገና ጨረታ አልወጣለትም፡፡
እኔ የተፈለቀቅሁት ከገዛ ጥጥ ማሳዬ ነው፡፡
እነሱ ሊያባዝቱኝ ከንቱ ይደክማሉ፡፡
አለም ደግሞ (ቁሌታም) እንዝርት ናት፤….ለሰበቃት ጭን ምትገልጥ!....
እሷ……….
እኔ………..
እነ’ሱ…
ሥጋት ላይ ተወዝቼ እሰማለሁ እኔ…(እሷ ጆሮ ዳባ ብላለች፡፡)
እነሱ መች ያርፋሉ…ቅኝቱ እንደፈረሰ ሙዚቃ ጣም አጥተው፡፡
                         ***
ከጆሮዬ ጥግ ከዐይኔ ፊት ቆመው… “አንተ ደግሞ ሽንፈትን አሜን ብለህ ለመቀበል ትልሞሰሞሳለህ…!” ይሉኛል፡፡
ነፍሴ…እጅ እንደማትሰጥ አልገባቸውም፡፡
“ለኮረኮመህ ሁሉ ጉልበትህ እንዳገዳ ቅንጥስ የሚል ከሆነ፣ መቆምህ በራሱ መውደቅ ነው!” ይሉኛል፡፡
ነፍሴ…እጅግ ታጋሽ ሆና፣ ትዕግስትን፣ እንደመልካም ሰባኪ ከልቤ አውደምህረት ላይ ትሰብከኛለች፡፡
“መታገስ ማለት ምን ማለት ነው…! ማንን ነው ምትታገሰው…ጊዜ ጊዜ የሚሰጥህ ይመስልሃል…?! ወደ ኋላ ተመልሶ እጅህን እየጐተተ “ና” የኔ ውድ ያለፈህን አምሃ ላገናኝህ…እንዲልህ ትመኛለህ…! እ….” ወደፊት ካልተራመድክ በቆምክበት ሙጃ ይበቅልብሃል ይሉኛል፡፡…አንደኛችን በሌሎኛችን ኪሮሽ የምንደነተል ዳንቴሎች እንሆናለን…? ልክና መጠን የለንም እንዴ!
ነፍሴ….በጥሞና ትተነፍሳለች… “ተዋቸው…መሰንበት ደግ ነው በጤና ድጉስ ተለብጦ…” እያለች የትዕግስትን ጠበል ትፀብለኛለች፡፡
“ጊዜው የመንፈስም የአካልም ትግል በብርቱ የሚጠይቅ ነው!...ድከም ልፋ…ላብህን አትመልከት… ኋላ ላይ ላብህ ፍሬ ይሆናል…” ይሉኛል፡፡
ሰው ሆነን “ሰው አርገኝ እና ሰው ይግረመው” አይነት ቀሽም ጥቅስ ይጠቅሱልኛል፤ ባመንበት ቅንብብ ህይወት ደስታ ትገዛለች፡፡
ነፍሴ…”ምርጦች ፍጡር ነን” ትለኛለች፣ ነፍሴን አምናታለሁ…እሷ ግን ትጠረጥረኛለች፡፡ ከሀጢያት በቀር ሁሉም ተፈቅዷል፡፡ አውቃለሁ፡፡ ያውቃሉ። (እናውቃለን)
እኔ በቆምኩበት ልክ መቆም ሳይሆን በኔ መቆም ላይ መገኘት እስካልተቻለ ድረስ፣ ይሄ ነው ተብሎ እሚደመደም ምንም ሊኖር አይገባም፡፡
የኔ ልክ የገዛ ራሴ ብቻ ነው፡፡ ሚስቴ ራሷ በልኬ አልተሰፋችም!
(ዋስትናውን እኔ ወስዳለሁ … እኔ ነኝ ያልኩት)፡፡
ጥርሴ ላይ የተነቀስኩት (ድዴ ላይ) የተዘጋባትን ተስፋ ነው፡፡
ወሬ አይኑን ሥር ኩል በደማቁ ተኩሎ…ከንፈሩን በቀለም አሳብዶ ጆሮ ጥግ የሐጢያት ዘፈኑን ያቀነቅናል፡፡
                          ***
እንዲህ ስልቹ ሰው እንደዘመዘመው ነጠላ…ጊዜ በከፋው ቁጥር ብስክስክ እያለ ባለበት ጊዜ “ሰው” እንዴት ከለሰለሰ እና ከረሰረሰ ብሎም ደጋግሞ ከታረሰ ምቹ ገላ ላይ እየተንፈላሰሰ…ሁለት ሆኖ ወድቆ…ሶስት መሆን ያቅተዋል…? እልና…
ነፍስ…
ህሊና…
ሥጋ…
ሙግት ውስጥ ገብተው ለጠብ ሲዳረጉ መገላገል ያቅተኛል፡፡
ነፍሴ... የተበጀችበትን ጉልህ ጠብታ አባዝታ ባህር ማድረግ እንደምትችል እየገባት እንዳልገባት ሆና፣ ያልገባውን ህሊናዬን በስስ ሥጋ ተለብጦ እያየችው ትስቅበታለች፡፡ ህሊናና ሥጋ ቀለማቸው የመንታ መንገድ ነው፡፡አንድ ይሆኑና አንድ ያይደሉ…በአንድ ግንድ የበቀሉ ቅጠሎች (ልምላሜው እንደሚለያይ አይነት፡፡)
ነፍስ ከሳቀች ደግሞ ሥጋት ነው፡፡ ሥጋ በተስፋ መቁረጥ ራሱን መጐሰም ይሳነዋል፡፡
ህሊናዬ…የሚያየውን እና የሚሰማውን ለነፍሴ ከማቀበሉ በፊት በጣም ለሚወደው ስሜቴ ያማክረዋል፡፡ …ስሜቴ የወጣለት ዱርዬ ነው! (ሥጋ ቅብ ነገር) ከሴት ልጅ የተለያዩ ብልቶች የተሰራ ይመስል…ሴት” ሲባል ብቻ መላ አካሉ ዐይን ሆኖ ይባትታል፡፡ እሚያመዛዝንበት ጭንቅላትም ይሁን ልብ ስላጣ በ“ነገ” ልስልስ ምንጣፍ ለመቀመጥ “ዛሬ”ን ማጨንገፍ አይመቸውም፡፡
ስሜቴ በቅንፍ መኖር ያዘወትራል፡፡
በሥጋ ተገዢነት አንቀልባ ላይ መኖር ጅልነት ነው፡፡
ነፍሴ ግን ድሎቷን ረግጣ ጠፍንጋ ለመቀየድ እስከ ጥጉ ጥግ ድረስ ትሰደዳለች፡፡
በቆምኩበት መጠን ሳይመጠኑ…ያለ እረፍት ይወተውቱኛል፡፡
እንዳገባ…እንድወልድ…(ትዳር ስለቱ ሶስት ነው)
ቀለሙም ከቀስተደመና ያይላል…(እይታ ያሻዋልና…)
ሞኞቹ…ትዳር እንዴት ነው ሲሏቸው “በጊዜ ግባና ፍርፍር ይበዛዋል” ይላሉ፡፡ በሶስት ቀለም ባሸበረቀ ጥለት እቅፍ ውስጥ መኖር ደግሞ ጣዕሙ እንደ ኗሪውና አኗኗሪው ነው፡፡ ጣዕሙን ለመግለጽ ለማብራራት እማይችሉት እንደጡብ ድርድር ስትር ያለ፣ የማዕዘን ድንጋዩን አርአያነት መመልከት ነው። በተለያየ አቅጣጫ፡፡ ቀለሙ እንዲህና እንዲያ ይገለጣል፡፡
አንደኛ…በጋራ ህይወትን ለመኖር ነው…(እየኖርኩ እየኖርን ነን…)
ሁለተኛ…ፍትወተ ሥጋን ለመፈፀም ነው…(ለጋ ቂቤ ጣል ያለበት ጣት ሚያስልስ ፍትፍት እስኪመስለኝ(ን) ተመችቶኛል (ናል)
ሶስተኛው…ዘርን ተክቶ ለማለፍ ነው…(ማን ዘርቶ መሰብሰብ ይጠላል)…
እንግዲህ “እምቢልኝ”! ያቃተኝ ጉዳይ ይሄው ነው፡፡ ዘር ዘርቶ ፍሬ ለመልቀም መልካም ገበሬዎች የዘሩትን (ፍሬ) መመልከትም ሌላ (ፍሬ) ነው፡፡ መዝራት ያልቻሉ ደካሞች (የዘር ፍሬ) የሌላቸው…በተዘሩት፣ የዋናው ገበሬ ፍሬዎች መደመም ይችላሉ፡፡ በግድ ያለጊዜውና ያለወቅቱ በማጨጃ ጊዜ መዝራት ሳይቻልስ…በዘር ጊዜ ለማጨድ…ያለደንቡ…?!...
                                    ***
ተደባልቆባቸው…
በቆምኩበት ቦታ ላይ ያልተለኩ…ይጠዘጥዙኛል፤
ኧረ ተውኝ ወዳጆቼ…”እሺ” የሚለው ቃል ምላሴ ላይ የተነቀሰ ይመስል ያሉኝን (ያለችኝን) “እሺ” ከማለት የዘለለ ምንም አማራጭ የለኝም። “እሺ” ደግሞ ብዙ የቆሰሉ ስህተቶችን የማከም ጥበብ አለው፡፡ ያለቦታው ሲገኝ ብቻ ነው “እሺ” መረር የሚለው፡፡ ልክ ገመዱን እንደበጠሰው ጐሽ!...
“አግባ እንጂ”
“ምነው እስከዛሬ…”
“ቆሞ መቅረት አማረህ”
“አማርጣለሁ ስትል ተመርጠህ እንዳትቀር”
“አግባ…አግባ አግባ” ሲሉኝ የነበሩት ሁሉ የቡና መጠጫ ሲኒ አላዋጡም፡፡ እምንሰጠው የምንችለውን ብቻ ሳይሆን ተቀባዩም መቻል አለመቻሉን ማወቅ ይኖርብናል፡፡ ያለፈው … ሳያንሳቸው “የዳይፐር” ዋጋ መናሩን ሳያውቁ (ከዚህ ጋር አንድ የሃገሬ የፊልም ዳይሬክተር ትዝ አለኝ፡፡ ሩጫዬ በዳይፐር ነው ያለው)
“ውለድ እንጂ … ተው ኋላ ትቆጫለህ!” ይሉኛል (ናል)፡፡
ሥጋዬ (ህሊናዬም አብሯት አለ) ነጋሪት ሥትጐሥም … ነፍሴ ፀሎት ላይ ናት፡፡ (ብቻዋን ተደማ)፡፡
የዘንድሮ ልጅ እንደ እኛ ዘመን በአንሶላ ቅዳጅ የሚያድግ መሠላቸው … እንዴ …? በአንሶለ ቅዳጅ ማደጉን ቢያውቅ ፍርድ ቤት ከመገተር ወደ ኋላ አይልም፡፡ በጨርቅ አሻንጉሊት ሠርተን ብንሠጠው … ራሱን አያጠፋም …?
እኛ የኔታ ጋ በሳርም ሆነ በአሳር ካርቶን ላይ በተለጠፈች ፊደል … የዛሬ እንጀራችንን ቆጥረናል። ዳዊት … ውዳሴ ማርያም … ብዙ ሌላ ነገሮች ሸምድደናል፤ አንዳንድ በማይመለከታቸው በሆነ ባልሆነው በኩርኩም ሲቆጉን … ፊደሎቹ ከአንጐላችን ዛፍ ላይ እየረገፉ መነመኑ እንጂ፡፡
እና … የአሁን ልጅ (ትውልድ) ፊደል ያዝና በሥንጥር እየጠቆምክ “ተማር” ብንለው በሥንጥሩ አይናችንን አይጠነቁለውም…!
በምን አባቴ(ታችን)… እንዲህ አይነት ኃላፊነት ውስጥ እገባለሁ … (እንገባለን?) ፍርሃት መፍትሔ እንዳይደለ ይገባኛል ገብቶኝም ያንገበግበኛል። ይህው … ተከራይቼበት ካለሁት ጊቢ የአከራዮቼ የልጅ ልጆችና እንደኔ የተከራዩ ልጆቻቸው ሲጫወቱ … የኔ ቢጤው የወለዳቸው … “አስር አረንጓዴ ጠርሙሶች በግድግዳ ላይ…” እያሉ በዜማ ሲጫወቱ እነዛ የአመት ቀለብ መግዣ ለአንድ ወር ተከፍሎላቸው “ወዛም” ትምህርት ቤት የሚማሩት የአከራዩን የልጅ ልጆች በስጨት ብለው … “ኤጭ የምን አስር አረንጓዴ ነው … አስር ላፕቶፖች በሉ…” ሲሏቸው አብሬ ከልጆቹ ጋር ተሸማቀቅሁ … አንጀቴ ተንቦጫቦጨ … ጨዋታ ለመቀየር ብለው … “እቴሜቴ የሎሚ ሽታ …” አሁንም እነዛ “ወዛም” ልጆች ተበሳጩ “ቢዮንሴ የት ሔዳ ነው … እቴሜቴ የምትሉት…?” የጐረቤቴ ልጆች የወፍጮ ቤት ግድግዳ መሠለ ፊታቸው፡፡
እሚያውቁትን ለማለት እንኳ መብት አጡ … “በዛ በበጋ በዛ በሙቀት … እጮኛ ጠፍቶ በፍለጋ…” ግጥምና ዜማውን ሳይጨርሱት “ወዛሞቹ” እጮኛ ምንድነው …? ማለት … ለሥንቱ ጥያቄ መልሥ ይኖራል …? …
የዚህ ዘመን ትውልድ ባንድ ተቃኝቶ የተዘበራረቁ የኑሮ ዜማ የሚያወጣ … በዋለበት የትምህርትም ( ) እማይሞላ ቅንፍ አዝለን … ከፍታውን የሚያጐላ … ማን ዝቅን ይወዳል፡፡
ነፍስ …
ህሊና …
ሥጋ …
በ “እምቢኝ” ማለት ሙግት ውስጥ ቡጢ ተቧቅሠው በሥጋት የምሥቅበት ጥርሴ ረግፏል፡፡ ግማሽ ሰብዕና የት ድረስ ያስኬዳል …?
ቅድመ ጋብቻ … ጓደኛ በሽበሽ! … ወሬው ቋንጣ ፍርፍር ይመስል … ይጥም ነበር፡፡ ምክር ባይነት ባይነት እንደገፍ ይሠነዘራል … “ነበር” ባይሆን፡፡፡
የልቤ የሚሉት ጓደኛ … ልብዎን ሰጥተውት ልቡን የሚያውቁት … ካገባ በኋላ የሚስቱን ሻሽ (ተሻሽቶ) አስሮ … እንዴት አድርጋ ብታስፈራራው እንደሆነ ባልታወቀና ባልተጠና ጥናት … ለማማከርም … እንትፍ እንትፍ የሌለውን የጓደኝነት ንጡ ጠላ ለመጐንጨት በሚስት የማስፈራራት ቡጢ ትከሻው ኮስምኖ … አለመገኘትን ያዜማል፡፡ (ሚስቶች ግን ለምን እንዲህና እንዲያ ይሆናሉ…?!) “እንዴት …?” እንዳትሉኝ!
                                 ***
“አግባ እንጂ” ማግባቴን ያላወቁ፡፡
“አገባሁ እኮ” እየተሽኮረመምኩ እመልሳለሁ፡፡
“ወለድክ” ቃሉ ካፈጣጠኑ እንደ ኩርኩም ያማል፡
“አ.ል.ወ.ለ.ድ.ኩም፡፡” አቀርቅሬ በዐይኔ መሬት እየጫርኩ እመልሳለሁ፡፡
ራስን መሆን …
ራስን ማዜም …
ለራስ ጊዜ ሠጥቶ … ራስን ብቻ መቃኘት አይቻልም …?
በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የምንወረውራቸው የቃል ጠጠሮች የብዙኃኖችን ዐይን ያጠፋሉ። የቀኙን ለግራው … የግራውን ለቀኙ ሥናደርግ የሚመጣው መንሻፈፍ አይነት!
“ለምን ታዲያ አልወለድክም እስከዛሬ…?”
“በፒን ኮድ ቆልፋው!” እላለሁ … በቀልድ እነሱን ለማሳቅ ራሴን ከማሳቀቅ ለመታደግ፡፡
እርግጥ ነው … የወንድ ልጅ ፍላጐት የፈለገ የደን ሠደድ እሣት ቢሆን በሴት ልጅ አለመፈለግ ጥቂት ምራቅ ይጠፋል፡፡
“እና ፒን ኮዱን ማወቅ አቃተህ…? ታዲያ አንተ ምኑን ወንድ ሆንከው!”
ይሔ ሥድብ ነው…? ምክር ነው…? መልካም ምኞት?...
ነፍስ … እውነቷን ለማንም አሣልፋ አትሠጥም፡፡
ህሊና … ይሉኝታ ያሸንፈዋል፡፡
ሥጋ … ልክሥክሥ ነው፡፡
ነፍስ፣ ህሊና፣ ሥጋ፣ ማንንም አትስሙ
በነቀፌታ እንቅልፍ … ደንዝዟል አለሙ፡፡
                                     ***
በታመመው ሰው አልጋ ላይ መተኛት ህመሙን መጋራት ማለት አይደለም፡፡ በባለ ጉዳዩ ሰንጠረዥ ውስጥ ማጥቆር …
እንደ ዝንጀሮ መጐርመሱን ለማወቅ እንደሚሻው፣ ባባቱ መዳፍ ምልክት መዳፉን ለክቶ ሲገጥምለት ለመጋጠም (በትዕቢት) እንደሚያጓው … ብዙ ብዙ ብንልም ህይወት እንዲህ አይደለችም፡፡
ባለመግባት ውስጥ ያለውን ነፃነት የሚያውቀው ለነፃነቱ የታመነው ነው፡፡
በመውለድና ባለመውለድ መካከል ያለው ገደል የትኛውም ተራራ ከየትም ሀገር ተነቅሎ መጥቶ ቢጠቀጠጥ አይሞላውም፡፡ ሸራፋ ደስታ አለ…? ህይወት እንዲህ አይደለችም!!!
ራስን መውለድ ይቻላል፡፡ አጥብቀው ያሰሩትን ሲፈቱት የታሰረበት ቦታ መልክ አለው፡፡ ፊት ላይ ያለ ጠባሳ ማለት ነው፡፡ እንደማይከልሉት፡፡
“እምቢኝ” የምለው (ንለው) አብረን ከሆነ … ከጥያቄው ውስጥ መልሱ አለ፡፡ በማንም ቡሃቃ ማንም ሊጥ አያቦካም፡፡ እያንዳንዱ ቡሃቃ … ልክ እና አዛዥ አለው፡፡
“እምቢኝ” ሥሜት ወለድ ምክርን!
“እምቢኝ” የሥጋት ጥሪን …!
“እምቢኝ” ብዙ ፍሬፈርስኪ ነገሮችን …!
“እምቢኝ” ቅን አልባነትን …! እምቢኝ … እምቢኝ!
“እሺ” ነፍሴን አምናታለሁ፡፡
                                  ***
ቀናት ያልፋሉ ሳምንትን ፀንሰው
ወር እየወለዱ ባመት ሊያሳድጉ፣
ዘር መተካት ብቻ ነው
የሰው ልጅ ማዕረጉ፡፡

Published in ልብ-ወለድ

        “ፓርቲው የህዝቡ ነው፤ ህዝቡ ደግሞ የፓርቲው”

             የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ሻርል ደጎል፤ ጊኒ ከሌሎች የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ከነበሩ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ተለይታ እቅዳቸውን በመቃወም ነፃነቷን በመምረጧና መሪዋ አህመድ ሴኩቱሬም ባደባባይ ክብራቸውን በማዋረድ ለፈጸሙት ድፍረት ተገቢ ነው ብለው የወሰዱት በተለያዩ የመንግስትና የግል የስራ መስኮች ተሰማርተው የነበሩትን ፈረንሳውያን ከጊኒ የማስወጣት የበቀል እርምጃ አለንጋው የጊኒና የሴኩቱሬን ጀርባ ሰምበር በሰምበር እንዳደረገውና ህመሙም ክፉኛ እንደቆጠቆጣቸው በሚገባ ተገንዝበውት ነበር፡፡ እናም ጊኒም ሆነ መሪው ሴኩቱሬ የበቀሉ አለንጋ የፈጠራቸውን ከፍተኛ የህመም ስሜት መቋቋም ስለማይችሉ ባጭር ጊዜ ውስጥ “አባታችን ፓፓ ደጎል ወይ ! ሳናውቅ በስህተት አውቀንም በድፍረት በሰራነው ስህተት እጅግ በጣም ስላስቀየምንዎት ፤በተለምዶው ፈረንሳዊ የአባትነት ቸርና ሩህሩህ ልብዎ እባክህ ይቅር ይበሉን፤ ከዚህ በኋላ እንዲህ ያለ ድፍረት በፍፁም አይለምደንም! መጀን ለእርሶና ለታላቋ ፈረንሳይ አገዛዝ!” በማለት ይቅርታ ይጠይቃሉ፡፡

ከዚያም ያወጁትን ነፃነት በመቀልበስ ይመሰረታል የተባለው የፍራንኮ - አፍሪካ ኮሚኒቲ አባል በመሆን፣ በፈረንሳይ አገዛዝ ስር ለመኖር ይወስናሉ ብለው በእርግጠኛነት ጠብቀዋቸው ነበር፡፡ ለፕሬዝዳንት አህመድ ሴኩቱሬ ግን ይህ የሚሞከር ሳይሆን ጭራሽኑ የሚታሰብ ነገር አልነበረም፡፡ ያጋጠማቸው ፈርጀ ብዙና ውስብስብ ችግሮች ከፍተው ከቁጥጥር ውጪ እንዳይሆኑ በውስጣቸው የተፈጠረው ስጋት ልባቸውን በጭንቀት ሊያቆመው ደርሶ ነበር፡፡ ነገር ግን በህዝባቸውም ሆነ እንደ ቀንደኛ ጠላት በሚቆጥሯቸው ፈረንሳዊያን ዘንድ ተሸናፊና ተንበርካኪ መስለው ለመታየት ፈፅሞ ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ይህ ችግርና ፈተና ጊዜያዊ እንደሆነና መፍትሄ እንደሚያፈላልጉለት ለህዝባቸው ቃላቸውን መስጠታቸውን አላቋረጡም ነበር፡፡

ይህንን ተከትሎም ለጎረቤቶቻቸው ሀገራት መሪዎች የድረሱልኝ የእርዳታ ጥሪያቸውን አቀረቡ፡፡ ይሁን እንጂ እህ ብሎ የሰማቸው አልነበረም፡፡ ሁሉም “ስራህ ያውጣህ! እዚያው በፀበልህ እንደ ፍጥርጥርህ!” በማለት ጥሪያቸውን ጆሮ ዳባ ልበስ አለባቸው፡፡ የድረሱልኝ የእርዳታ ጥሪው በቀጥታ ባይደርሳቸውም ጉዳዩን በወሬ ወሬ ሰምተው አስር ጋናውያን መምህራንና አስር ነርሶችን የላኩላቸው ቀድሞውኑም “ግንባር ቀደሙ የትግል ጓዴ” እያሉ የሚጠሩዋቸውና በጣም የሚያደንቋቸው የጋናው ፕሬዝዳንት ክዋሜ ንክሩማህ ብቻ ነበሩ፡፡ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውሱ ከእለት ወደ እለት እየከፋ እጅግ አደገኛ አቅጣጫን መከተል ሲጀምር፣ በጐረቤቶቻቸው የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት “አይንህን ላፈር” ተብለው የተገለሉት ፕሬዝዳንት ሴኩቱሬ፤ ፊታቸውን ወደ ምዕራብ አለም ማዞር እንደማያዋጣ አልጠፋቸውም፡፡ መያዣ መጨበጫ በሌለው ሁኔታ ምስቅልቅሉ የወጣው የጊኒ ሁኔታ የጊኒውያኑን የዕለት ተዕለት ህይወት ፈታኝ ቢያደርግባቸውም የነፃነታቸው አባት መሪያቸው ሴኩቱሬ፤ ቃል በገባላቸው መሰረት ችግራቸውን ባፋጣኝ እንደሚፈታላቸው በመተማመን በከፍተኛ ትዕግስት በተስፋ ጠብቀዋቸዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ሴኩቱሬ ግን ያደረጉት ጥረት “የቅኝ ገዢዎች ቡችሎች” ያሉዋቸው የጎረቤት ሀገሮች መሪዎች ባደረሱባቸው መገለልና ፈረንሳይ ግንባር ቀደም ተዋናይ የሆነችበት የምዕራቡ ኢምፔሪያሊዝም ነፃነታቸውን መልሶ ለመቀማት በፈፀሙባቸው “ታላቁ ሴራ” ሳቢያ እንዳልተሳካላቸው ለህዝባቸው ይፋ አደረጉ፡፡ በመጨረሻም ፈረንሳይና የምዕራቡን አለም “የኢምፔሪያሊዝም አድርሆት ሀይል” በሚል ክፉኛ ካወገዙ በሁዋላ፣ ፊታቸውን ወደ ሶቪየት ህብረትና ሌሎች ሶሻሊስት ሀገራት አዞሩ፡፡ ህዝባቸውን በኮናክሪ የነፃነት አደባባይ ከሰበሰቡ በሁዋላም እንዲህ ሲሉ ንግግር አደረጉላቸው፡- “ቅኝ ገዢው የፈረንሳይ መንግስትና የምዕራብ ኢምፔሪያሊዝም ነፃነታችንን ዳግመኛ ለመቀማት በማሰብ፣ በፈፀሙብን ሴራ ለከፍተኛ ችግር ተዳርገናል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የቅኝ ገዥዎችና የኢምፔሪያሊዝም ቡችላ በሆኑ አድሀሪ መንግስታት በአራቱም ማዕዘን ዙሪያችንን ተከበናል፡፡

ስለዚህ የተጋረጠብን አደጋ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ነፃነታችንንና ሉአላዊነታችንን ከምዕራብ ቅኝ ገዢዎች ግዙፍ መንጋጋ ውስጥ በትግላችን መንጭቀን እንዳወጣነው ሁሉ አሁን የገጠመንን ችግርም አምርረን በመታገል እንወጣዋለን፡፡ ልብ አድርጉ ይህ ችግር የገጠመን በባርነት ለመኖር አሻፈረኝ ስላልንና ጦርነት ስር ሆነን በምቾትና በድሎት ለመኖር ፈቃደኞች ስላልሆንን ብቻ ነው፤ እኛ ጊኒያውያን በባርነት ውስጥ ከሚገኝ ምቾት ይልቅ ነፃነታችንን ተጎናፅፈን በድህነት ለመኖር የመረጥን ነፃነት ወዳድ ታጋይ ህዝቦች እንደሆንን መቼም ቢሆን እንዳትዘነጉ፡፡ ከቅኝ ገዢዎችና ከኢምፔሪያሊዝም እግር ስር እስክንበረከክ ድረስ እስከ እድሜ ልካችን እንደማይተኙልን እንዳትረሱ፡፡” ፕሬዝዳንት ሴኩቱሬ ንግግራቸውን ሲያጠናቅቁም፤ “ሞት ለቅኝ ገዢዎች! ሞት ለምዕራብ ኢምፔሪያሊዝምና አድርሆት ሀይላት! የጊኒ ነፃነት ለዘላለም ይኑር!” በማለት መፈክር አሰሙ፡፡ ህዝቡም መፈክሮቹን አብሮአቸው ካሰማ በሁዋላ፣ “ቪቫ ቱሬ”፣ “ቪቫ ቱሬ” እያለ በከፍተኛ ድምፅ በመጮህ ለእሳቸው ያለውን ፍቅር ገለፀላቸው፡፡

ይህ በሆነ በሶስተኛው ቀን ፕሬዝዳንት ሴኩቱሬ፤ በሶቪየት ህብረትና በሌሎች የምስራቅ አውሮፓ ሶሻሊስት ሀገራት ይፋ ያልተገለፀ የሁለት ሳምንት ጉብኝት አድርገው ተመለሱ፡፡ እግራቸው የሀገራቸውን ምድር መርገጡን ተከትሎም በሺዎች የሚቆጠሩ የምስራቅ አውሮፓ የአስተዳደር ባለሙያዎች፤ ዶክተሮች፣ ነርሶችና ሌሎች የህክምና ባለሙያዎች፤ ኢንጅነሮች፣ ቴክኒሻኖችና መምህራኖች ወደ ጊኒ ጎረፉ፡፡ ቀኑ ቀንን እየገፋ ወደ ፊት በተጓዘ ቁጥርም ከቁጥጥር ውጪ ወደ መሆን ተቃርቦ የነበረው ምስቅልቅል ሁኔታ ቀስ በቀስ ወጥ መስመር እየያዘ መሄድ ጀመረ፡፡ የጊኒን ሁኔታ በጥሞና ይከታተሉ የነበሩ የአፍሪካና የተለያዩ ሀገራት ህዝቦች ፕሬዝዳንት ሴኩቱሬን “ለቅኝ አገዛዝና ለምዕራብ የአድህሮት ሀይላት ያልተበገረ ጀግና!” ሲሉ አወደሷቸው፡፡ ድፍን ጊኒያውያን ደግሞ “አይበገሬው የነፃነት አባታችን! ካንተ ቀድመን እኛ እንሙትልህ!” በማለት ዳር እስከዳር እልል አሉላቸው፡፡ ከምስራቅ አውሮፓ የመጡት ባለሙያዎች የፈረንሳይን ባለሙያዎች መውጣት ተከትሎ የተፈጠረውን ከፍተኛ ምስቅልቅ ሙሉ በሙሉ መቅረፍ ባይችሉም ካሁን አሁን ፈነዳ ሲባል የነበረውን የጊኒን ልብ በመጠኑም ቢሆን ተግ ማድረግ መቻላቸውን የተረዱት ፕሬዚዳንት አህመድ ሴኩቱሬ፤ ወዲያውኑ የወሰዱት እርምጃ የሴኩቱሬና የሴኩቱሬ ብቻ የሆነ የአመራር ስርአትን መዘርጋት ነበር፡፡

እናም በቢሮአቸው ውስጥ በልዩ ረዳትነት ሲያገለግሏቸው የነበሩትን አራት የሩማኒያ የፓርቲና የመንግስት አስተዳደር ባለሙያዎች፣ በሻይ ዕረፍት ሰአት ወደ ቢሮአቸው ጠርተው ሻይ ጋበዟቸውና በተሰባበረ እንግሊዘኛ እንዲህ ብለው ጠየቋቸው፡- “ሰማችሁ ጓዶች! ታላቁ የሩማኒያ ህዝባዊ አብዮት በኮሚዩኒስት ፓርቲው ጠንካራ አመራር የምዕራብ አድርሆት ሀይላት የደቀኑበትን በርካታና ውስብስብ ችግሮችን ተቋቁሞ አመርቂ ድሎችን እንደተቀናጀ ይታወቃል፡፡ ለመሆኑ የሩማኒያ ኮሚኒስት ፓርቲ የጥንካሬው ምንጭ ከቶ ምንድን ነው?” እነሱም የስላቪክ ቋንቋ ቃና ባደላበት አነጋገር እንዲህ በማለት መለሱላቸው፡- “ጓድ ሊቀመንበር! ታላቁ የሩማኒያ አብዮት በኮሚኒስት ፓርቲው ጠንካራ አመራር የተቀናጀውን በርካታ አንፀባራቂ ድሎች መረዳት መቻልዎት የሚያረጋግጠው አንድ ታላቅ ቁምነገር፣ ምን ያህል አርቆ አሳቢና ባለብሩህ አዕምሮ መሆንዎን ነው፡፡ የሩማኒያ ኮሚኒስት ፓርቲ ዋና ፀሃፊ ጓድ ኒኮላይ ቻውቸስኮም የላቀ አርቆ አሳቢና የምጡቅ አዕምሮ ባለቤት ናቸው፡፡

ታላላቅ አብዮተኞች ተመሳሳይ ባህሪ እንዳላቸው ይህ ተጨባጭ ማስረጃ ነው፡፡ ጓድ ሊቀመንበር! የሩማኒያ ኮሚኒስት ፓርቲ ለታላላቅ ድሎች የበቃበት የጥንካሬው ምንጭ በዋናነት የአመራሩ ጥንካሬና ህዝባዊ መሰረቱ ነው፡፡ ፓርቲው የህዝብ ነው፤ ህዝቡ ደግሞ የፓርቲው ነው፡፡ “የሩማኒያ ህዝብ ከኮሚኒስት ፓርቲው በቀር ሌላ ፓርቲ ያልፈለገበት ምክንያት የምዕራብ አድርሆት ሀይላት እንደሚያስወሩት የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን በመቃወም ሳይሆን በዚህ የተነሳ ብቻ ነው፡፡ ፓርቲው የህዝብ ፓርቲ በመሆኑ ህዝቡ ምን እንደሚያስፈልገው፣ ምን አይነት ሀሳብ ማሰብና ምን አይነት ውሳኔ መወሰን እንዳለበት አስቀድሞ በማሰብ ይወስንለታል፡፡ የኮሚኒስት ፓርቲው ምን አይነት የትግል መስመርና አቅጣጫ መከተል እንዳለባት የሚወስኑ የፖሊት ቢሮና የማዕከላዊ ኮሚቴ አሉት፡፡ የእነዚህ ሁለት ኮሚቴዎች ዋነኛ አንቀሳቃሽ ሞተርና የህይወት እስትንፋስ ደግሞ ጓድ ዋና ፀሃፊ ኒኮላይ ቻውቸስኮ ብቻ ናቸው፡፡ በቃ ምስጢሩ ይሄው ነው፡፡ ከዚህ ሌላ ምንም ነገር የለም ጓድ ሊቀመንበር ሴኩቱሬ!” ፕሬዝዳንት ሴኩቱሬ እንደዋዛ ለጠየቁት ጥያቄ ያገኙት መልስ ከበቂ በላይ ነበር፡፡ ከሩማንያ ረዳቶቻቸው ያገኙት ምክር የወደፊት የአመራር መስመርና አቅጣጫ የጠቆማቸው ነበር፡፡

ሴኩቱሬ ረዳቶቻቸው የሰጧቸውን ይህንን ምክር ለቀናት ቢሮአቸውን ዘግተው ለብቻቸው ሲያወጡና ሲያወርዱ ከቆዩ በሁዋላ፣ የጊኒና የህዝቦቿን ቀጣይ እጣፈንታ የወሰኑበትን የአመራር ስርዓታቸውን የዘረጉበትን አራት ወሳኝና ከፍተኛ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ውሳኔዎችን በመወሰን በተግባር ለመተርጎም ባጭር ታጥቀው ተነሱ፡፡ ፕሬዝዳንት ሴኩቱሬ ካሳለፏቸው አራት ውሳኔዎች ውስጥ የመጀመሪያው “የምዕራባዊያንንን የኢምፔሪያሊዝምና የኮሎኒያሊዝም የአድህሮት ሀይላት በምዕራብ አፍሪካ ሳያሰልሱ መዋጋት” የሚለው ነው፡፡ ይህንን ውሳኔአቸውን በተመለከተ በተደጋጋሚ የተጠየቁት ፕሬዝዳንት ሴኩቱሬ፤ የሰጡት መልስ፤ ግንባር ቀደም የአፍሪካ ፀረ ኮሚዩኒዝም ትግል መሪ እንደመሆናቸው መጠን ያላቸውን ታሪካዊ ሃላፊነት ለመወጣት የወሰኑት ውሳኔ እንደሆነ በማስመሰል ነበር፡፡ ግን ትክክለኛው ምክንያታቸው ይህ አልነበረም፡፡ የዚህ ውሳኔ ኢላማ አሜሪካ ወይንም እንግሊዝ አልነበሩም፡፡

ፈረንሳይና ፈረንሳይ ብቻ እንጂ፡፡ ፕሬዚዳንት ሴኩቱሬ፤ ጊኒ ነፃነቷን ለመጎናጸፍ በወሰደችው እርምጃ የተነሳ በተለያዩ መንግስታዊና የግል የሙያ መስክ ተሰማርተው ጊኒን እንደሃገር ቀጥ አድርገው አቁመው ይዘዋት የነበሩትን በሺ የሚቆጠሩ ፈረንሳዊያንን በማስወጣት የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ሻርል ደጐል የወሰዱት የበቃል እርምጃ ያደሠረባቸው ጉዳት ህመሙ ከሚችሉት በላይ ነበር፡፡ ከምስራቅ አውሮፓ የተላኩላቸው ባለሙያዎች ተፈጥሮ የነበረውን እጅግ አደገኛ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ምስቅልቅል ከሞላ ጐደል ቢቀርፉላቸውም የጀርባቸው ላይ ቁስል ገና በወጉ አላጠገገም ነበር፡፡ በዚህ የተነሳም በፈረንሳይና በፕሬዚዳንት ደጐል ላይ የቋጠሩት ቂም በቀል እየተንከተከተና አንዳንዴም እየገነፈለ እረፍት ይነሳቸው የነበረው በየእለቱ ነበር፡፡ ለፕሬዚዳት ሴኩቱሬ በቀል ማለት ልክ እንደ ዝናብ ማለት ነበር፡፡ ዝናብ ሲዘንብ ደግሞ የአንድን ቤት ጣራ ብቻ ለይቶ አይመታም፡፡

ፕሬዚዳንት ሴኩቱሬ፤ ፈረንሳይና ፕሬዚዳንቷን ሻርል ደጐልን መልሰው ለመበቀል በእጅጉ ቋምጠው ነበር፡፡ ይህን የበቀል ጥማቸውን ለማርካትም ፕሬዚዳንት ደጐል ከፅንስ እስከ ውልደቱ ዋነኛ ተዋናይ የሆኑበትን የፍራንኮ-አፍሪካ ኮሙኒቲን ለማፍረስ ይህ ቀረሽ የማይባል ዙሪያ መለስ የፖለቲካ ትግልና የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ከፈቱ፡፡ ዝሆን የፈለገውን ያህል ከሲታ ቢሆን በሚኖርበት ጫካ ውስጥ ከሱ የበለጠ ግዙፍ እንስሳ እንደ ሌለ በሚገባ ያውቃል ይባላል፡፡ ፕሬዚዳንት ሴኩቱሬም በጊኒ ብቻ ሳይሆን በምዕራብ አፍሪካ ደን ውስጥ ያሉት ዝሆን እርሳቸው እንደሆኑ ለፈረንሳይና ለፕሬዚዳንት ደጐል ለማሳየት የምድሩን ድንጋይ ሁሉ ገለበጡት፡፡

በፊት የፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ ቡችሎች እያሉ ይዘልፏቸው የነበሩትን የሴኔጋሉን መሪ ሊዎፖልድ ሴዳር ሴንጐርንና፣ የኮትዲቯሩን መሪ ፌሊክስ ሁፌት ቧኘን ሳይቀር በወዳጅነት በመጋበዝ፣ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ህዝቦች የፍራንኮ-አፍሪካ ኮሙኒቲን በማፍረስ ከፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ ለመላቀቅ ትግላቸውን እንዲያጧጡፉ ጥሪያቸውን አቀረቡ፡፡ የፈረንሳይ ኢኮኖሚያዊ እርዳታ ከተቋረጠብን ምኑን ከምን ልናደርገው ነው በሚል ሲጨነቁና ሲጠበቡ ለነበሩት የምዕራብ አፍሪካ ግንባር ቀደም ፖለቲከኞች “ፍርሀት መቼውንምና በየትኛውም ቦታ ቢሆን ሞትን አስቀርቶት አያውቅም” አሏቸው፡፡ ፕሬዚዳንት ሴኩቱሬ እንኳን ሌሎቹ ፈረንሳውያን ራሳቸውም እንኳ እስኪያንቃቸው ድረስ የጀመሩትን ፀረ-ፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ ትግልና ከፍተኛ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ አጠናክረው ገፉበት፡፡

እንዲህ ሆኖም ግን ፈረንሳውያንና ፕሬዚዳንታቸው የፕሬዚዳንት ሴኩቱሬን የፀረ-ፈረንሳይ ዘመቻ በቀላሉ እንደማይሳካ በመተማመን ዘና ብለው ነበር፡፡ ክፉኛ መሳሳታቸውን ያወቁት 1960 ዓ.ም በባተ በሁለተኛው ወር የፈረንሳይ አፍሪካዊ የበኩር ልጅ በመባል የሚታወቁት የሴኔጋሉ መሪ ሴንጐር፤ ሀገራቸውንና ያኔ ሱዳን ተብላ የምትጠራውን ማሊን በፌዴሬሽን አዋህደው፣ ከፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ ነፃ ለመውጣት ጥያቄያቸውን እንዳቀረቡ ነው፡፡ ፕሬዚዳንት ደጐል፤ በሀገራቸው እጅ በምርጥ የፈረንሳይ ትምህርት ቤቶች እየተማሩ ተቀማጥለው ያደጉትና በኋላም የፈረንሳይ ካቢኔ አባል ሚኒስትር የነበሩት ቀንደኛው አፍቃሬ ፈረንሳይ ሴዳር ሴንጐር ያቀረቡት የነፃነት ጥያቄ የፈጠረባቸው ግርምትና ድንጋጤ ገና ሳይለቃቸው ሌላ ሁኔታ ተከትሎ መጣባቸው፡፡ በአቢጃንና በኮናክሪ ሁለት ጊዜ በሚስጥር በመገናኘት ለረጅም ሰአታት ከፕሬዚዳንት አህመድ ሴኩቱሬ ጋር ሚስጢራዊ ውይይት አድርገዋል እየተባለ ውስጥ ውስጡን ሲታሙ የነበሩትና የፍራንኮ-አፍሪካ ኮሙኒቲ መመስረቻ የፈረንሳይ አምስተኛው ሪፐብሊክ ህገ መንግስት ግንባር ቀደም አርቃቂ የነበሩት “ባለ ጥቁር ቆዳ ፈረንሳዊው” የኮትዲቯሩ መሪ ሁፌት ባኘም የሀገራቸውን የነፃነት ጥያቄ በይፋ ለፈረንሳይ መንግስት አቀረቡ፡፡ ካሜሩንና ቶጐም፣ ሴኔጋልንና ኮትዲቯርን ተከትለው የነፃነት ጥያቄአቸውን አቀረቡ፡፡

አዲስ ፀረ-ፈረንሳይ የነፃነት እንቅስቅሴ በምዕራብ አፍሪካ በፍጥነት መቀጣጠል ጀመረ፡፡ ፕሬዚዳንት ሴኩቱሬም ሌሎች የምዕራብ አፍሪካ ሀገራትም እንደ ካሜሩንና ቶጐ የፀረ-ፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ ትግላቸውን እንዲያፋፍሙና የነፃነት ጥያቄአቸውን እንዲያቀርቡ በመገፋፋት በከፍተኛ ሁኔታ ትግላቸውንና ቅስቀሳቸውን አፋፋሙ፡፡ የተፈጠረው ሁኔታና ጊዜው ለፈረንሳይና ለፕሬዚዳንት ደጐል አዲስና አስቸጋሪ ነበር፡፡ ሀገራቱ ያቀረቡትን የነፃነት ጥያቄ በእሽታ ከማስተናገድ በቀር አፍነው ሊያስቀሩት የሚችሉበትም ሆነ ፕሬዚዳንት ሴኩቱሬን በድጋሚ የሚበቀሉበት አቅም ጨርሶ አልነበራቸውም፡፡ እናም አንጋፋ ምኒስትሮቻቸውን ስነስርአቱን እንዲከታተሉ የፈረንሳይ ወኪል አድርገው በመላክ ለካሜሩንና ለቶጐ ከፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ ነፃነታቸውን እንዲቀዳጁ ፈቀዱ፡፡ በምዕራብ አፍሪካ የተቀጣጠለው የነፃነት ትግልና የፕሬዚዳንት አህመድ ሴኩቱሬ የፀረ-ፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ ቅስቀሳ ግን በቀላሉ የሚገታ አልነበረም፡፡ ከማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ እስከ ሞሪታኒያ፤ ከሴኔጋል እስከ ቻድ በመላ የምዕራብ አፍራካ ሀገራት፣ የነፃነት ትግሉ ዳር እስከ ዳር መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡ ይህም በምዕራብ አፍሪካ ተዘርግቶ ለበርካታ ዘመናት የዘለቀው የፈረንሳይ የቅኝ አገዛዝ ፀሀይ እንደጠለቀችና ግብአተ መሬቱ በእጅጉ እንደታቀረበ የሚያመለክት የመጀመሪያው የማስጠንቀቂያ ደወል ሆነ፡፡

የ1960 ዓ.ም ነሀሴ ወር አሀዱ ብሎ ግም ካለበት ጀምሮ በቀጣዮቹ ሀያ ቀናቶች ብቻ ዘጠኝ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ከፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ ነፃ ወጡ፡፡ ምኒስትሮችና ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦች ያሉበት የፈረንሳይ ልኡካን ቡድንም በቤኒን፣ ኒዠር፣ ቡርኪናፋሶ፣ ኮትዲቯር፣ ቻድ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ኮንጐ ብራዛቪል፣ ጋቦንና ሴኔጋል የፈረንሳይ የቅኝ አገዛዝ ባንዲራ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሲወርድ በእማኝነት ለመታዘብ በየእለቱ ከአንዱ ከተማ ወደሌላኛው ቀልባቸውን አጥተው ሲዋከቡ ከረሙ፡፡ በዚሁ አመት የመስከረምና የጥቅምት ወራትም ማሊና ሞሪታንያ ከፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ በመላቀቅ ነፃነታቸውን አወጁ፡፡ የበቀል ጥማቸው የረካውና አንጀታቸው ቅቤ የጠጣው ፕሬዚዳንት ሴኩቱሬ፤ በልባቸውም ቢሆን ፕሬዚዳንት ደጐልን “እኔ ሴኩቱሬ እንዲህ ነኝ! የልቤን ሰራሁልህ!” ማለታቸው አልቀረም፡፡ በአፍሪካና በምስራቁ አለምም የፀረ ኢምፔሪያሊዝምና ኮሎኒያሊዝም ጀግና ታጋይ በመባል በዝና ላይ ዝና ደረቡ፡፡ በሀገራቸዉ ውስጥም ጊኒያውያን “ቆራጡ መሪያችን! የኢምፔሪያሊዝም ውጋት! የኮሎኒያሊዝም መጋኛ!” በማለት በእልልታና በሆታ ጨፈሩላቸው፡፡ የመጀመሪያው እቅዳቸው በተሳካ ሁኔታ እንደተከናወነ እርግጠኛ የሆኑት ፕሬዚዳንት ሴኩቱሬም ሌላ ጊዜ አላጠፉም፡፡ ወደ ሁለተኛው እቅዳቸው ተሸጋገሩ፡፡ በሊቀመንበርነት የሚመሩትን የጊኒ ዲሞክራቲክ ፓርቲን የህዝቡ ፓርቲ፣ ህዝቡንም የፓርቲው ማድረግ፡፡ ይህን እቅዳቸውን ለማሳካትም ከዚህ የሚከተሉትን ድርጊቶች ፈፀሙ፡፡ የሳምንት ሰው ይበለን፡፡ እንመለስበታለን፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ
Saturday, 22 June 2013 11:32

ቢጫ ካርድ እና ቢጫ ወባ

ከላቦራቶሪው ውጤት ይልቅ የብሔራዊ ቡድኑ ውጤት ነው ያጓጓው፡፡ ጓደኞቹ ከስቴዲየም ደውለው ስለ ተመልካቹ ወረፋ አጋነው ነገሩት፡፡ ህዝቡ ለነገው ጨዋታ ከዛሬ ጀምሮ ሰልፍ ይዟል፡፡ ስጋት ገባው። እሱ ክሊኒክ ውስጥ ቁጭ ብሎ የምርመራ ውጤቱን ሲጠባበቅ፣ ስቴዲየሙ ሊሞላ ይችላል፡፡ የጓጓለትን የብሔራዊ ቡድኑን ጨዋታ በስቴዲየሙ ተገኝቶ ላይመለከት ይችላል፡፡ ሰአቱን ተመለከተ፡፡ ከምሽቱ አንድ ሰአት ከሩብ ይላል፡፡ ከዚህ በላይ መጠበቅ አልቻለም፡፡ ከክሊኒኩ ወጥቶ ወደ ስቴዲየም ሄደ - ቢኒያም፡፡

                                               ***

 ድል የጠማው ህዝብ፡፡ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ የለበሰ … አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ የተቀባ … ከ21 ሰአታት በላይ ወረፋ ጠብቆ ወደ ስቴዲየሙ ለመግባት የወሰነ ተመልካች፡፡ የነገውን የብሔራዊ ቡድኑን ድል ለማጣጣም ጓጉቶ በጋለ ስሜት “ማታ ነው ድሌ” የሚል ተሰልፎ አዳሪ ደጋፊ፡፡ የአዲስ አበባ ዝናብ የማይቀዘቅዘው፣ ትኩስ ስሜት በደም ስሩ የሚዘዋወር የአዲስ አበባ ኳስ አፍቃሪ፡፡ ቢኒያም ከዚህ ተመልካች ጋር ነው፡፡ እያጨበጨበ፣ እየዘመረ፣ እየዘፈነ … ብርድ እያንዘፈዘፈው፣ ወጨፎ እየገረፈው፣ … ሌሊቱ እስኪጠባ፣ ሰአቱ ደርሶ ስቴዲየም እስኪገባ፣ ቡድናችን ጐል እስኪያገባ ጓጉቶ (ህመሙን ረስቶ)

                                                  ***

 ብሄራዊ ቡድኑ አሸነፈ፡፡ አገር በደስታ ስታብድ አምሽታ አደረች፡፡ ቢኒያምም ከአገር ጋር ሲያብድ ውሎ ብቻውን ሲሰቃይ አደረ፡፡ “ኑሮ ወሸባ”ውን ጨርሶ ወደ ቤቱ ሲገባ ወባው ተነሳችበት፡፡ ቅዳሜ ምሽት የላብራቶሪ ውጤቱን ሳይቀበል ወደ ስቴዲየም መሄዱን ያስታወሰው ሰኞ ጠዋት ነው፡፡ ህመሙ ሲያገረሽበት፡፡ ህመሙ ሲጠናበትና የሰራ አካላቱ በላብ ሲዘፈቅ ወደ ጓደኞቹ ደወለ፡፡ “ድረሱልኝ” አላቸው፡፡ ደረሱለት፡፡ ብሔራዊ ቡድናቸውን በልዩ ሁኔታ ደግፈው ከድል እንዳደረሱት፣ ጓደኛቸውን ቢኒያምንም በአግባቡ ደግፈው ክሊኒክ አደረሱት፡፡ *** የክሊኒኩ ግቢ በትርምስና በውዝግብ ታመሰ። የውዝግቡ ሰበብ ለቢኒያም አዲስ የታካሚ ካርድ አውጡ፣ አናወጣም የሚል ነው፡፡ የቢኒያም ጓደኞች “ቅዳሜ እለት አውጥቶ ስለተመረመረ ለአዲስ ካርድ መክፈል አይገባንም” ሲሉ ተከራከሩ፡፡ ያለፈው የምርመራ ውጤት ውድቅ ተደርጐ ተጨማሪ ዋጋ እንድንከፍል መደረጉ አግባብ አይደለም በማለት ተሟገቱ፡፡ የክሊኒኩ አስተዳዳሪ ጉዳዩን ለማጣራት ሞከሩ፡፡

                                                         ***

የላብራቶሪ ቴክኒሻኑ፡- ቅዳሜ ዕለት የቢኒያምን ደም መርምሬ ቢጫ ወባ እንዳለበት በማረጋገጥ ለሚመለከተው ሃኪም ውጤቱን ልኬያለሁ፡፡ እኔ ተጠያቂ አይደለሁም፡፡ ውጤቱን አይቶ የቢጫ ወባ ስላለብህ ስቴዲየም መሄድ የለብህም ማለትም ሆነ ጥንቃቄ እንዲያደርግ መምከር የሃኪሙ ሃላፊነት ነው፡፡ ሐኪሙ፡- ቢኒያም ቢጫ ወባ እንዳለበት የሚገልፀው ወረቀት በወቅቱ አልደረሰኝም፡፡ ቢደርሰኝ ኖሮ ወደ ስቴዲየም እንዳይሄድ በማሳሰብ እረፍት አድርጐ እንዲያገግም አደርግ ነበር፡፡ ነርሷ፡- በእለቱ ከላቦራቶሪ የተላከው የምርመራ ውጤት እንደደረሰኝ አልክድም፡፡ ይሄም ሆኖ ግን በወቅቱ ስራ በዝቶብኝ ስለነበር፣ ወረቀቱ የት እንደገባ ሳላውቀው ጠፍቶብኛል፡፡ ለሐኪሙ ወረቀቱን ባለማድረሴ ጥፋተኛ ነኝ፡፡ ቢኒያም፡- በወቅቱ የምርመራ ውጤቱን አይተው “ቢጫ ወባ ስላለብህ ወደ ቤትህ ሄደህ ማገገም እንጂ ወደ ስቴዲየም መሄድ የለብህም” ማለት የነበረባቸው ሐኪሙ ናቸው፡፡ እርግጥ እኔም ብሆን በተደጋጋሚ የያኋቸውን የቢጫ ወባ ምልክቶች በማስታወስ፣ ስቴዲየም ከጓደኞቼ ጋር ከመሰለፍ ይልቅ ወደ ቤቴ ሄጄ ማረፍና የሚታዘዝልኝን መድሃኒት መውሰድ ይገባኝ ነበር፡፡ ጓደኞቹ፡- ሐኪሙም ሆኑ ሌሎች የክሊኒኩ ሰራተኞች ቢኒያም ቢጫ ወባ እንዳለበት እያወቁ ነው፣ ህክምናውን ሳይጨርስ ወደ ስቴዲየም እንዲሄድና እንዲሰለፍ የፈቀዱለት፡፡ የክሊኒኩ ሰራተኞች፡- እንግዲህ ምን እናድርግ! … ችግር እንደሚገጥመው ብናውቅም ጓደኞቹ በጉጉት እየጠበቁት እንደሆነ እያወቅን “አትሂድ”፣ “አትሰለፍ” ለማለት ከበደን፡፡ በመጨረሻ ሁሉም በአንድነት የጋራ መግለጫ ሰጡ። “ስህተት ሰርተናል!”

Published in ልብ-ወለድ

“ከተማውን ሁሉ እንኩሮ አደረጉት!” - የመዲናዋ ነዋሪ ምሬት

              አዲስ አበባ ከተማ በ126 ዓመት ታሪኳ እንደአሁኑ በልማት ሥራ የተዋከበችበት ዘመን ያለ አይመስለኝም፡፡ ጅምር የልማት ሥራዎቹን ውጤት በተስፋ የሚጠብቁ፣ በአድናቆት የሚመለከቱ፣ ነቀፌታ የሚሰነዝሩ ፣ በቅሬታ የሚያዩ---ነዋሪዎች አሉ። የአመለካከት ልዩነት መኖሩ አልሚው አካል በአግባቡ ከተጠቀመበት ለልማት ሥራው መሻሻል የሚያበረክተው በጎ አስተዋጽኦ እንዳለው አያጠራጥርም፡፡ በከተማዋ ሲንቀሳቀሱ ግሬደር የማይፈነጭበት፣ አካፋና ዶማ ያላረፈበት መንደር ማግኘት ያስቸገራቸውና በተለይ በትራንስፖርቱ መጨናነቅ የተበሳጩ አንዲት ወይዘሮ ምሬታቸውን የገለፁት “ከተማውን ሁሉ እንኩሮ አደረጉት” በማለት ነው።

እንዲህ መሰሎቹ ቅሬታዎች በተለያዩ መድረኮችና የመገናኛ ብዙኃን ሲነገሩ በተደጋጋሚ ይሰማል፡፡ አዲስ አበባ “እንኩሮ” የመሆኗ ጉዳይ፤ አቶ አርከበ ዕቁባይ በከንቲባነት ዘመናቸው “ዘጠኝ ድስት ጥዶ…” በሚል በሥራ ጓደኞቻቸው ተተችተዋል የተባሉበትን ክስተት ያስታውሳል፡፡ አሁን የሚታየው እንኩሮስ በትክክል በስሎ ይወጣል ወይ? ብሎ መጠየቅ ተገቢ መሆኑ ፈፅሞ አያጠያይቅም፡፡ “ከተማውን ሁሉ እንኩሮ አደረጉት” የሚለው አባባል በአንድ በኩል አሉታዊ ቢመስልም በሌላ በኩል ግን ሥራና ጥረትን መኖሩንም አመላካች ይመስለኛል፡፡ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል በ1993 ዓ.ም ያሳተመው የአማርኛ መዝገበ ቃላት “አነኮረ” ከሚለው መነሻ ግስ ቀጥሎ “እንኩሮ” ለሚለው ቃል ካቀረባቸው ትርጉሞች አንደኛው “በውሃ ተበስብሶ በምጣድ ላይ እየተገለበጠ እንዲበስል የተደረገና ለጠላ የሚሆን ዱቄት” በሚል ይተረጉመዋል፡፡

ስለዚህ አዲስ አበባ ከተማ “እንኩሮ” የመሰለችው የበሰለና የተሻለ ነገር ለማስገኘት መሆኑ ቢያስደስትም ማንኮሪያው በማን እጅ ነው የተያዘው? የሚለው ግን ብዙ የሚያወያይ ነው፡፡ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሩ አቶ መኩሪያ ኃይሌ በቅርቡ ከኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቀርበው በሰጡት ቃለ መጠይቅ፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው የበላይ ተቆጣጣሪ ቢሆንም ውሃና ፍሳሽ፣ መንገደኞች ባለስልጣን፣ መብራት ኃይል፣ ቴሌኮሙኒኬሽን…መሥሪያ ቤቶች የየራሳቸውን ሥራ በየራሳቸው መንገድ እንደሚሰሩ ገልፀዋል፡፡ ይህ ደግሞ የከተማው “እንኩሮ” በተለያዩ አካላት እየተነኮረ መሆኑን ያመለክታል፡፡ የሥራ ክፍፍሉ ግድ መሆን ያለበትና ተገቢ ቢሆንም በሂደቱ የሚገኘው ውጤት ግን እርስ በእርሱ የማይናበብና የማይግባባ መሆኑ ትልቁ ችግር ይመስለኛል፡፡ ለዚህ እውነታ ብዙ ማሳያዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡

ከመስቀል አደባባይ ቦሌ የሚደርሰው አፍሪካ ጐዳና በአዲስ መልክ ከመሰራቱ ጥቂት ዓመታት በፊት የመንገድ አካፋይ (ፓርኩን) ለማስዋብ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ የወጣበት ሥራ ተሰርቶ ነበር፡፡ ሁለቱ ፕሮጀክቶች እንዲናበቡ ያልተደረገው ለምን ይሆን? በመንገዱ ግራና ቀኝ ተነጥፎ የነበረው “ኮብል ስቶን” ከአፈር ጋር ተዝቆ ሲነሳ ስለባከነው ሀብትስ ቀደም ብሎ ማሰቡ ሳይቻል ለምን ቀረ? በአዲስ አበባ ከተማ በቅርቡ ሥራቸው ተጠናቆ ከተመረቁ መንገዶች መካከል ከልደታ ደሴ ሆቴል ወደ ካርል አደባባይ የሚያደርሰው መንገድ አንዱ ቢሆንም፤ መንገዱ ደሴ ቡና ቤት አካባቢ ለአዲስ ሥራ ግሬደሮች እየተርመሰመሰበት ነው፡፡ በልደታ አካባቢ፤ መስቀለኛ መንገድ ላይ እየታየ ያለው አዲስ ቁፋሮ ከባቡር መስመር ዝርጋታው ጋር ሊያያዝ እንደሚችል መገመት ቢቻልም በመንገዶች ባለስልጣን ስር ያሉት ሁለት ሥራዎችስ እርስ በእርስ መግባባት እንዴት አቃታቸው? የሚያስብል ነው፡፡ በ22 አካባቢ የሚኘው ትራፊክ ጽሕፈት ቤት አዲስ ሕንፃ ገንብቶ ካስመረቀ ሁለት ዓመት ያለፈው አይመስለኝም፡፡

ከሲ ኤም ሲ ወደ ጦር ኃይሎች የሚዘረጋው የባቡር መስመር በ22 በኩል ስለሚያልፍ የትራፊክ ጽሕፈት ቤት አዲሱን ሕንፃ የግንብ አጥርና ወደ ሕንፃው የሚያስገቡ ደረጃዎችን ከሰሞኑ እያፈረሰ ይገኛል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ መሪ ፕላንን ዳግመኛ የማሻሻል ሥራ ለማከናወን የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ስለመሆኑ ሲነገር ሰንብቷል፡፡ በ1995 ዓ.ም ነባሩ ማስተር ፕላን ተሻሽሎ ሲፀድቅ ከሲ ኤም ሲ እስከ ጦር ኃይሎች የባቡር መስመር ዝርጋታ እንደሚኖር ተጠቁሞ ነበር፡፡ ሕጉ፣ አዋጁ፣ መመሪያው…ቢኖርም አንዱ ከሌላው ጋር እርስ በእርስ የመናበብ ችግር ስለሚታይበት የትራፊክ ጽሕፈት ቤት ሕንፃ ሲሰራ ቦታው ከባቡር መስመር ዝርጋታ ጋር በተያያዘ እንደሚፈለግ የሚያመለክት ስላልተገኘ ለጉዳት መደረጉ እውን ሆኗል፡፡ ለዚህ ጥፋት ተጠያቂ ሊሆን የሚችለው ማነው? በሙቀጫ የተገኘውን ሁሉ በአንድነት መውቀጥ እንዳይሆን ሕጐችን፣ ትዕዛዞችንና መመሪያዎችን ጠብቆ መሥራት ያስገኘውን ጥቅም ማመልከት ተገቢ ይመስለኛል፡፡ በጊዮርጊስ በኩል ወደ መርካቶ የሚዘልቀው የባቡር መስመር ዝርጋታን መሠረት ያደረገ ነበር ይዞታዎችን የማፍረስ ተግባራት እየተከናወኑ ነው፡፡

የመዘጋጃ ቤት አጥር፣ የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት፣ “ቁጭራ ባንክ ቤት” የነበረበት የመርካቶው ጥንታዊ ሕንፃና የክፍለ ሀገር መናኸሪያ የመሳሰሉት ተቋማት የፈረሱም በመፍረስ ሒደት ላይ ያሉም አሉ፡፡ በዚህ መስመር ከመፍረስ የዳነው አዲስ ሕንፃ እንዴት ከመፍረስ ዳነ? በ1990ዎቹ አጋማሽ ግንባታው የተጀመረውና ሀብተጊዮርጊስ ድልድይ አካባቢ የሚገኘው “ተፈራ ስዩም የገበያ ማዕከል” ሕንፃ ከሰሞኑ የማፍረስ ሂደት መትረፍ የቻለው የ1995 ዓ.ም መሪ ፕላንን ተከትሎ ከዋናው መስመር ገባ ብሎ መገንባት በመቻሉ እንደሆነ መገመት አያስቸግርም፡፡ ለዚህ መሰሉስ አርቆ አሳቢነት ምስጋናውን መቀበል ያለበት ማነው? ከአዲስ አበባ ልማት ጋር በተያያዘ አስተማሪ ተሞክሮ በመለገስ መርካቶ ያበረከተችውን ትልቅ አስተዋጽኦ በዚህ አጋጣሚ ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ የመርካቶ ነባር ይዞታዎች ፈርሰው በአዲስ የመተካት ሥራ የተጀመረው በ1996 ዓ.ም ቦንብ ተራ የሚገኘው አንድ ብሎክ በማፍረስ አዲስ ግንባታ ሲጀመር ነበር። አሁን አዲስ ፋና ኃ.የተ.የግ.ማ የሚገኝበት ባለ 8 ፎቅ ሕንፃ የተሰራበት ቦታ ላይ የሚገኝ አንድ ብሎክ የፈረሰ ዕለት ፍራሹን በመርካቶ ዙሪያ ባሉ መንደሮች ወስዶ የመድፋት ተግባር ተፈጽሞ ነበር፡፡

ብዙም ሳይቆይ ግን መገንባት ብቻ ሳይሆን ማፍረስም ሥራና ካፒታል ሊፈጠርበት እንደሚችል ለሌሎች ትምህርት የሚሆን ተግባር ያሳየችው መርካቶ ነበረች፡፡ አሁን በአዲስ አበባ ከተማ ለዳግም ልማት የሚፈርሱ ቤቶች ለሥራ ፈላጊዎች አንዱ ሥራ ማስገኛ መፍትሔ ሆኖ ቀርቧል፡፡ ማፍረሱም፣ ፍርስራሹን መሸጡም፣ ገቢ የሚያስገኝ ሥራ ሆኗል። ከልማት ሥራ ጋር በተያያዘ እንዲፈርሱ በመደረግ ላይ ያሉት አሮጌ ቤቶችና የደከሙ መንደሮች ብቻ ሳይሆኑ ነባር ትላልቅ ሕንፃዎችንም በመንካት ላይ ስለሆነ አፈራረሱን አንድ ደረጃ ማሳደግ ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡ ከሲ ኤም ሲ ወደ ጦር ኃይሎች ለሚዘረጋው የባቡር መስመር ሥራ እንዲፈርሱ ተወስኖባቸው ተግባራዊ በመሆን ካሉ ነባር ሕንፃዎች ሁለቱ ለገሀር መስቀለኛ መንገድ ላይ ይገኛሉ፡፡

ሕንፃዎቹን የማፍረሱ ሥራ በሰው ኃይል እየተከናወነ ይገኛል። አገሪቱ እርካሽ የሰው ኃይል ስላላትና ያንንም መጠቀም ስለሚኖርባት ሕንፃዎችን ለማፍረስ ይህንን ኃይል መጠቀም አስፈላጊ ነው ካልተባለ በስተቀር ሕንፃዎችን በሳይንሳዊ ጥበብ ወደ ብናኝነት መለወጫ ዕውቀቱ ያለው ባለሙያ አይጠፋም፡፡ በከተሞች ከሚታየው የልማት ሥራ ጋር በተያያዘ የተከሰቱ ችግሮችን ለመቅረፍ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር፤ የሕግና የፖሊሲ ማዕቀፍ ማዘጋጀት ስለሚቻልበት ሁኔታ በያዝነው ሳምንት አንድ ስብሰባ በሒልተን ሆቴል አካሂዷል፡፡ የሚወጣው ሕግና ፖሊሲ በልማት ሥራ “እየተነኮረች” ባለችው አዲስ አበባ፤ ማንኮሪያውን ለመያዝ ዕድል የሚያገኙትን አካላት በጥብቅ የሚቆጣጠር ብቻ ሳይሆን ተጠያቂም የሚያደርግ መሆን አለበት፡፡ መንገዶች ሲሰሩ ሕንፃዎች እንዲፈርሱ ከማድረግ ይልቅ ሕንፃዎች ሲሰሩ ማን ተከትሎ እንደሚመጣ ቀድሞ መታሰብ አለበት፡፡

አዲስ አበባ ከተማ አሁን በጀመረችው ፍጥነት እድገቷ የሚቀጥል ከሆነ መብራት ኃይል ባለስልጣን የኤሌክትሪክ ሽቦ ተሸካሚ ምሰሶዎችን ነቃቅሎ ጥሎ የመብራት መስመሩን በሙሉ መሬት ውስጥ መቅበር አለብኝ የሚልበት ዘመን መምጣቱ አይቀርም፡፡ እዚያ ዘመን ላይ ደርሰን ሕንፃና መንገድ በማፍረስ ሀብት፣ ጉልበትና እውቀታችንን ከማባከናችን በፊት ዛሬ ላይ አርቆ ተመልካች ያስፈልገናል፡፡ ማን ኮሪያው በማን እጅ ነው የተያዘው? ብዬ እንድጠይቅ ያነሳሳኝ ይህ ስጋት ነው፡፡

Page 5 of 17