ከ4.6 ሚሊዮን በላይ ህዝብ አደገኛ ርሃብ ተጋርጦበታል

    የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምግብ ፕሮግራም፤ ደቡብ ሱዳን በታሪኳ አስከፊ የተባለው የምግብ እጥረት እንደገጠማትና 40 በመቶው የአገሪቱ ህዝብ በመጪዎቹ ጥቂት ወራት አስቸኳይ የምግብ እህል እርዳታ እንደሚያስፈልገው መግለጹን ቢቢሲ ዘገበ፡፡

የእርስ በእርስ ግጭት፣ የምግብ ዋጋ መናርና እየተባባሰ የመጣው የኢኮኖሚ ቀውስ፣ በደቡብ ሱዳን ከፍተኛ የምግብ እጥረት መፍጠሩን ያስታወቀው የአለም የምግብ ፕሮግራም፣ 4.6 ሚሊዮን የሚሆነው የአገሪቱ ህዝብ በመጪዎቹ ሶስት ወራት አስከፊ ርሃብ ላይ ይወድቃል ብሏል፡፡

እያሽቆለቆለ የመጣው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ችግሩን በአፋጣኝ ሊያባብሰው እንደሚችል ያለውን ስጋትም ገልጾ፣ አለማቀፉ ማህበረሰብ በአገሪቱ የተከሰተውን የምግብ እጥረት ለመፍታትና ርሃቡ የሚያደርሰውን ጥፋት ለመቀነስ አስቸኳይ የምግብና የነፍስ አድን እርዳታ ማድረግ ይጠበቅበታል ሲልም ጥሪውን አቅርቧል፡፡

የምግብ እጥረቱ በተለይም የመንግስትና የአማጽያን ሃይሎች ተደጋጋሚ ግጭት ሲያደርጉባቸው በቆዩትና በርካታ ዜጎች በተፈናቀሉባቸው በጆንግሊ፣ አፐር ናይልና ኒቲ ግዛቶች የተባባሰ እንደሆነ ከትናንት በስቲያ ብሉምበርግ ዘግቧል፡፡

በአፐር ናይል ግዛት የታየው የግብርና ግብዓቶች እጥረት በምርታማነት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጥሯል ያለው የአለም የምግብ ፕሮግራም፣ በዚህም አገሪቱ በዘንድሮው አመት ማምረት ከሚገባት የጥራጥሬ እህል ምርት 249 ሺህ ሜትሪክ ቶን ጉድለት እንዲፈጠር አድርጓል ብሏል ብሉምበርግ፡፡

በደቡብ ሱዳን መንግስትና በአማጽያን መካከል በ2013 የተቀሰቀሰውና ተባብሶ የቀጠለው ግጭት፣ ከ2 ሚሊዮን በላይ የአገሪቱን ዜጎች እንዳፈናቀለም ዘገባው አስታውሷል፡፡

 -

 

 

 

Published in ከአለም ዙሪያ

 

 

 

     የባንክ ሒሳብ ደብተር ቁጥር ይፋ አድርገዋል

    የአገሪቱ ህገ መንግስት ከሚፈቅድላቸው ውጪ ለሶስተኛ ዙር በምርጫ ለመወዳደር መወሰናቸው ከፍተኛ ተቃውሞና የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ያደረሰባቸው የብሩንዲው ፕሬዚደንት ፔሪ ንኩሩንዚዛ፣ ህዝቡ ምርጫውን በገንዘብ እንዲደግፍ ጥሪ ማቅረባቸውን ሲኤንኤን ዘገበ፡፡

ከምርጫው ራሳቸውን እንዲያገሉ የሚደርስባቸውን ውስጣዊና ውጫዊ ጫና አልሰማም ብለው ለመወዳደር የቆረጡት ፕሬዚዳንቱ፣ አለማቀፉ ማህበረሰብ ለምርጫው ማስፈጸሚያ ቃል የገባውን የገንዘብ ድጋፍ ላለመስጠት በመወሰኑ ህዝቡ የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርግ በፌስቡክ ገጻቸው ጥሪ አድርገዋል፡፡

“የኔን በምርጫ መወዳደር የደገፍክ የአገሬ ህዝብ ሆይ!... ለምርጫው ስኬታማነት በፈቃድህ የቻልከውን ያህል የገንዘብ ድጋፍ አድርግ” ያሉት ፕሬዚዳንት ኑኩሩንዚዛ፣ ህዝባቸው ለምርጫው የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርግበትን የባንክ የሒሳብ ቁጥርም ይፋ አድርገዋል፡፡

የፕሬዚዳንቱ በምርጫ የመወዳደር ውሳኔ ይፋ መደረጉን ተከትሎ በአገሪቱ የተቀሰቀሰው ግጭት ያሰጋቸው ከ100 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ ጎረቤት አገራት መሰደዳቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ የተወሰነ መረጋጋት ቢፈጠርም ተቃውሞው እንደቀጠለ መሆኑንና ፕሬዚዳንቱም ምርጫውን በመጪው ሰኔ መጨረሻ ለማካሄድ መወሰናቸውን አክሎ ገልጿል፡፡

 

 

 

Published in ከአለም ዙሪያ

 

 

 

መንደርደርያ 

ካስቴል ወይን ጠጅ ፋብሪካ ባለፈው ግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ የተቋቋመበትን 1ኛ ዓመቱን በማስመልከት፣ የወይን ፌስቲቫል በዝዋይ ከተማ በፋብሪካው ቅጥር ግቢ ውስጥ  አዘጋጅቶ ነበር፡፡ ድርጅቱ በዚህ ፌስቲቫል ላይ የውጭ አገር ዜጎች፣ የካስቴል ወይን አከፋፋዮች፣ የባር ባለቤቶች  እንዲሁም   ጋዜጠኞችን የጋበዘ ሲሆን የወይን አጠማመቁን ሂደት ካሳየ በኋላ ተጋባዦቹን ብሉልኝ ጠጡልኝ ይል ጀመር፡፡ ወይን ጠጅ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስና ካስቴል ቢራ በገፍ ቀርቧል፡፡ 

 ጋዜጠኞች ምሳ ከበላን በኋላ እንደየፍላጐታችን ከቢራውም ከወይኑም አንድ ሁለት አልን፡፡ ኧረ የምን አንድ ሁለት? ከዚያም በላይ ተጐነጨን፡፡ ገሚሱ ጋዜጠኛ አቅሙን አውቆ መጠጣቱን አቆመና፤ “አንሄድም እንዴ?” ማለት ተጀመረ፡፡ ገሚሱ ደግሞ በሞቅታ “ወደ ቤታችን አይደለም’ዴ የምንሄደው? ምን አስቸኮለን? እንጠጣ እንጂ” አለ፡፡ በመጨረሻ  9፡30 ላይ እንደምንም ተሰባስበን ከፋብሪካው ወጣን፡፡ በአውቶብሳችን ውስጥ 6 ሰዎች ሊፍት ጠይቀው አብረውን ተሳፍረው ነበር፡፡

ባለ 5 ገቢሩ ድራማ የሚጀምረው ከዝዋይ ከተማ ወጥተን፣ ወደ አዲስ አበባ እየተጓዝን ሳለ ነው፡፡

መቸት

ቦታው ፡- ከዝዋይ አዲስ አበባ                     መስመር ላይ

ሰዓት፡- 9፡45 ገደማ

ተዋናዮች፡- ጋዜጠኞችና ሊፍት ጠይቀው              የገቡ እንግዶች

ክፍል 1፣ ገቢር 1

ተዋናዮች፡- ጋዜጠኛና እንግዳ

በልካቸው የጠጡ ጋዜጠኞች ወንበር ይዘው ተቀምጠዋል፡፡ ሞቅ ያላቸው ደግሞ በመተላለፊያው ወዲያ ወዲህ እያሉ ጮክ ብለው ከጓደኞቻቸው ጋር ያወራሉ፡፡ አንድ ፎቶ ጋዜጠኛ ፊት አካባቢ ከተቀመጠ ጓደኛው ጋር ይጫወታል፡፡ ሊፍት ጠይቀው ከገቡት ሰዎች መካከል የፊት ረድፍ ወንበር ላይ የነበረው እንግዳ ተሳፋሪ፣ የወንበሩን መደገፊያ ይዞ ቆሞ፣ ፎቶ ጋዜጠኛውንና ጋዜጠኛ ጓደኛውን  ቁልቁል ያያቸዋል፡፡

ብዙ አያስታውቅበትም እንጂ በደንብ ጠጥቷል፡፡ ፎቶ ጋዜጠኛው ኮስመን ያለ ነው፡፡ እንግዳው መካከለኛ ቁመትና ሞላ የተደላደለ ሰውነት አለው፡፡ አንዳንድ ሰው መጠጥ ሲቀምስ እውነተኛ ማንነቱ ገሃድ ይወጣል፡፡ ድብድብ ያምረዋል፡፡ እንግዳው ተሳፋሪ፣ ፎቶ ጋዜጠኛውን ሲመለከት፤“ይቺን ጪባ አንዴ በቴስታ ብላት አትዘረጋትም” የሚል ስሜት ሳያድርበት አልቀረም፡፡ እናም ያለምንም ማስጠንቀቂያ ፎቶ ጋዜጠኛውን በቴስታ እንካ ቅመስ አለው፡፡ ተመቺው አፀፋውን ለመመለስ ተነሳ፤ነገር ግን አፍንጫው እየደማ ስለነበር ተመልሶ ጐንበስ አለ፡፡ሁኔታውን የታዘብን ሁሉ እንግዳው ተሳፋሪ ላይ ጮህንበት፡፡ የስድብ መዓት አወረድንበት፡፡ ቆመው ከነበሩት ጋዜጠኞች መካከል ጥቂቱ፤ “ምንም ሳያደርገው እንዴት ይመታዋል?” በማለት ሰውየውን ለመምታት ተጋብዘው ነበር፤ ሌሎች  መሃል ገብተው ገላገሉ፡፡በዚህ ሁሉ መሃል ሰውዬው አንዲት ቃል አልተነፈሰም፡፡ ከእኔ ፊት 2ኛ ወንበር ላይ የተቀመጠ ሌላ እንግዳ ደግሞ ለተማቺው ማገዝ ፈልጐ ሲቁነጠነጥ ነበር፡፡

እንግዳው አናደደኝና በቁጣ ስሜት፤ “ሊፍት ለምኖ ገብቶ ምንም ያላደረገውን ሰው እንዴት ይመታል? ባለጌ ነው!” አልኩ፡፡ ከሰውየው ጐን ተቀምጣ ስትጨነቅ የነበረችው ሴት፣

“አዎ! እሱስ፤ ምንም ሳያደርገው መማታቱ ጥፋተኛ ነው፡፡ ሰክሮ’ኮ ነው” አለች፡፡

ይኼኔ አገርግሮ የነበረው ሰውዬ  ተረጋጋ፣ ፀቡም በርዶ መኪና ተንቀሳቀሰ፡፡ 

ባለ አንድ ገቢር፣ ሁለት

ተዋናዮች፡- ጋዜጠኞችና እንግዳ

5 ደቂቃ እንኳ ሳንጓዝ ነው ሁለተኛው ጠብ የተጀመረው፡፡ አሁንም ያው የመጀመሪያው ተንኳሽ ነው ጸብ የጫረው፡፡ ሰውየው ድምጹን አጥፍቶ ከመቀመጫው በመነሳት በእኔ ትይዩ 3ኛ ረድፍ ላይ የተቀመጠ የፎቶ ጋዜጠኛውን የቅርብ ጓደኛ ቡጢ አሳረፈበት፡፡ ለጓደኛው አግዞ ለምን ሰደበኝ ይመስላል፡፡ ደግነቱ ሰውየው ከአንድ ጊዜ በላይ አይሰነዝርም፡፡

ቡጢ ያረፈበት ጋዜጠኛ የአፀፋ ምላሽ ሰንዝሯል፡፡ በቀድሞ ድርጊቱ ተናደው የነበሩ ጋዜጠኞችም መጠጥ ባደከመው ጉልበት ቸብ ቸብ አድርገው ሲገፈትሩት፣ ስካር አድክሞት ስለነበር ሚዛኑን መጠበቅ አቅቶት የመኪናው በር ላይ በጀርባው ተዘረጋ፡፡ ሁለቱ  ተመቺዎችና አንድ ጋዜጠኛ፤ አንድ ሁለቴ በእግራቸው መቱት፡፡ “ኡኡ! ለሦስት ደበደቡኝ” አለና ፀጥ አለ፡፡በዚህ ጊዜ ሌሎች ጋዜጠኞች በቃ! በቃ! በማለት ልጆቹን ተቆጡና፣ሰውዬውን በሳንሳ ተሸክመው ከመኪናው በማውረድ ንፋስ እንዲያገኝ መንገድ ዳር በደረቱ አስተኙት፡፡ ሰውየው ለ10 ደቂቃ ያህል ቢተኛም ሊነቃ አልቻለም፡፡ ሰዓቱ ደግሞ እየመሸ ነው፡፡ ያወረዱት ጋዜጠኞች ተሸክመው መኪና ውስጥ በማስገባት የመጀመሪያው ረድፍ  ወንበሮች ላይ አጋደሙት፡፡

ክፍል አንድ፣ ገቢር ሦስት

ተዋናዮች፡- ጋዜጠኞች ጋዜጠኛ

 ሞቅ ያለው ሌላ ጋዜጠኛ ምንም ያልቀመሰ ለመምሰል እየሞከረ፣የተፈጠረውን ነገር ረስተን እየተዝናናን እንሂድ በማለት፣ከኪሱ ገንዘብ አውጥቶ እያሳየ፣“እዚች ላይ ያላችሁን ጠብ አድርጉ” እያለ ከፊት ጀምሮ ወደ ኋላ ገንዘብ መሰብሰብ ጀመረ፡፡ ብዙዎች በሐሳቡ አልተስማሙም፡፡ ስሙን እየጠሩ “ተቀመጥ ተቀመጥ” እያሉ ቢጮኹም እሱ ግን ተቃውሞውን ከመጤፍ  አልቆጠረውም፡፡ 

ዕቅዱ የሰመረለት አይመስልም፡፡ እኔ ጋ እስኪደርስ ራሱ ካወጣውና ሊፍት ጠይቃ የገባችው ሴት ከሰጠችው ገንዘብ በቀር ምንም አልያዘም፡፡ “የለኝም” ሲባል ዝም ብሎ ነው አልፎ የሚሄደው፡፡ እኔም ፈቃደኛ አለመሆኔን ሲያይ አልፎኝ በመሄድ፣መሃል ላይ እጅብ ብለው ወደቆሙት ሞቅ ያላቸው ጋዜጠኞች ሄደ፡፡ ከመቼው ከኋላ ጠብ እንደተነሳ እግዜር ይወቀው፡፡ ገንዘብ ሲጠይቅ የነበረው ጋዜጠኛ በቴስታ ከተመታው ፎቶ ጋዜጠኛ ጋር የስድብ ጥይት መወራወር ጀመሩ፡፡ ለዱላ ሲገባበዙ መሃል ገብተው ገላገሏቸው፡፡ አንደኛው ለገላጋይ እያስቸገረ፤ “እናትህ ---፤ አንት የሻዒቢያ ተላላኪ” ሲል ተሳደበ፡፡የጋዜጠኞቹ ሁኔታ ከቁጥጥሩ ውጭ የሆነበት የመኪናው ሾፌር፣ በሌላ አውቶቡስ ለተሳፈረው አስተባባሪያች ደውሎ የሆነውን ነገረው፡፡ ጠቡ በገላጋዮቹ በርዶ ጉዞ ጀመርን፡፡ ጥቂት እንደተጓዝን የፊት ረድፍ ወንበር ላይ የተጋደመው ሰካራም ቀና እንኳ ሳይል አስመለሰው፡፡ሦስቱ ፀቦች የተነሱት ከዝዋይ ተነስተን መቂ እስክንደርስ ነበር፡፡ ሰክሮ የተኛው ሰውዬ አልነቃ ስላለ ምናልባት አሞት ይሆናል በሚል መቂ ስንደርስ፣ ወደ ሐኪም ቤት ወሰድነው፡፡ የክሊኒኩ ሠራተኞች ሁኔታው ሲነገራቸው ለመተባበር ፈቃደኛ ሆኑና መኪናው ድረስ መጥተው፣ ሰውዬውን ከመረመሩት በኋላ ከስካር በስተቀር ምንም ችግር እንደሌለበት ነገሩን፡፡

ክፍል አንድ፤ ገቢር አራት

ተዋናዮች፡- የሚዲያ ኃላፊና ሊፍት ጠይቃ የገባች ወጣት 

ከክሊኒኩ እንደተመለስን መኪናችን ለጥቂት ጊዜ ቆም ብሎ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ሊፍት ጠይቀው ከገቡት ሰዎች መካከል መጨረሻ ወንበር ላይ የነበረችው ወጣት በተፈጠረው ነገር መናደዷን ገምቻለሁ፡፡ በዚያ ላይ የሚዲያ ኃላፊው አጠገቧ ቆሞ ይነዘንዛታል፡፡ ጠበሳ መሆኑ ነው፡፡ ቢቸግራት ከመኪናው ለመውረድ ተነሳች፡፡ ሃላፊው ይባስ ብሎ ማለፊያ መንገድ ዘጋባት፡፡ “አሳልፈኝ እንጂ” ስትል ጮኸች፡፡ ዞር ብዬ አየሁ፡፡ መንገድ የዘጋባት የማውቀው ጋዜጠኛ መሆኑን ሳይ፣ ስሙን ጠርቼ “አሳልፋት እንጂ” አልኩ፡፡ ዞር ብሎ አይቶኝ ምንም አላደረኳትም’ኮ በሚል ከበሬታ ፈገግ እያለ “እህቴ’ኮ ናት” አለኝ፡፡ “እህትህም ብትሆን ልለፍ ስትል አሳልፋት” አልኩትና መንገዱን ለቀቀላት፡፡ ትልቅ ሻንጣዋን አብሯት ከነበረው ልጅ ጋር ይዛ ለመውረድ ወደ በሩ ሄደች፡፡ በሩ ጋ  ደግሞ ሌላ ችግር ገጠማት፡፡

ክፍል አንድ፤ ገቢር አምስት

ተዋናዮች፡- ሌላ ፎቶ ጋዜጠኛና ወጣቷ እንግዳ

ግራና ቀኝ ባሉት የመጀመሪያ ረድፍ ወንበሮች ላይ በቴስታ ተማቺው ሰካራም ተጋድሟል፡፡ አጠገቡ ጥቂት ጋዜጠኞች ቆመዋል፡፡ አንደኛው ሌላ ፎቶ ጋዜጠኛ ነው፡፡ ወጣቷ ሰካራሙን ተራምዳ ለማለፍ ስትል ፎቶ ጋዜጠኛው ፊቷ ተገተረባት፡፡ ሊግባባት ፈልጎ ነበር፡፡ ወጣቷ በንዴት ብው! አለችና “አሳልፈኝ!” በማለት እንደገና ጮኸች፡፡ የጋዜጠኛውን ስም ስለማውቅ ጠርቼ፤ “አሳልፋት እንጂ” አልኩት፡፡

 ፎቶ ጋዜጠኛውም ፈገግ እያለ፤ “ምንም አላረኳትም’ኮ ሻንጣሽን ላሳልፍልሽ ነው ያልኳት” አለኝ፡፡ “ራሷ ታሳልፍ ተዋት” አልኩትና መንገዱን ለቀቀላት፡፡

ወጣቷ በንዴት ጦፋ ስለነበረ፣ ሻንጣዋን ካሳለፈች በኋላ፤“ስቱፒድ!” ብላ ሰድባው ወረደች፡፡ ፎቶ ጋዜጠኛውም እንዴት ትሰድበኛለች ብሎ በመጦፍ፣ ወጥቶ ሊደበድባት ሲጋበዝ፣ ውጭ የነበሩ ጋዜጠኞች ያዙት፡፡

                         ****** ******

መጠጥ በጣም መጥፎ ጠላትና አደገኛ አሳሳች ነው፡፡ ከልክ እንዳያልፍ ተቆጣጥረው በጥንቃቄ ካልጠጡ፣ በተገላቢጦሽ የሰዎችን አዕምሮ ይቆጣጠርና ተገዢው ያደርጋቸዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ይሉኝታ ይጠፋል፣ ማኀበራዊ ሕጐችና ደንቦች ይጣሳሉ፡፡ ሰው ምን ይለኛል? የሚል ስጋት ይጠፋና ጤነኛ ሆነው የማያደርጉትን ለመፈጸም ይገፋፋሉ፡፡

የሚዲያ ሃላፊው ጋዜጠኛ፤ ስለሴቶች መብት መከበር፣ ስለሴቶች እኩልነት፣ ሴት ልጅ ከፍላጐቷ ውጭ ምንም ዓይነት ፆታዊ ትንኮሳ (አቢዩዝ) ሊደረግባት እንደማይገባ ብዙ ጊዜ በሚዲያው እንደተናገረና እንዳስተማረ እገምታለሁ፡፡ ከመጠጥ በኋላ ግን ሁሉ ነገር ተረሳ፡፡  ሾፌሩ የደወለላት አስተባባሪያችን መኪናውን አስቁሞ፤ “ምነው እንደዚህ ሆናችሁ? አፈርኩባችሁ!” አለን፡፡ ያኔ አብዛኞቹ ጋዜጠኞች ስካሩ የበረደላቸው ቢሆንም ጥቂት ያልበረደላቸው የሚያደርጉት ነገር አስጠልቶኝ ነበር፡፡ ስለዚህ ከመኪናው ወርጄ “አፈርኩባችሁ” ያለን አስተባባሪያችን ወደነበረበት አውቶቡስ ለምኜ ገባሁ፡፡

ሁኔታው ያላማራቸው ጥቂት ጋዜጠኞች የመጀመሪያው ፀብ እንደተጀመረ ከኛ መኪና ላይ ወርደው በትራንስፖርት መመለሳቸውን፣ የሰከረው ሰውዬ ነቅቶ ምንም ሳይናገር ዝም ብሎ መቀመጡን፣ ሳሪስ ሲደርስም ጋዜጠኞቹን “ክፉ አይንካችሁ” ብሎ መውረዱን በማግስቱ ሰማሁ፡፡

 

 

 

 

Published in ህብረተሰብ

 

 

 

ኢህአዴግ በተቃዋሚዎች “ባዶ ውጤት” አፍሯል ወይም ተፀፅቷል!

    የዘንድሮ 5ኛው አገራዊ ምርጫ በኢህአዴግ ጠቅላይ አሸናፊነት የተጠናቀቀ ይመስላል፡፡ (ቅድመ ትንበያ ተከልክሏል ለካ!) የእኔ ግን ቅድመ ትንበያ ሳይሆን መረጃ ላይ የተመሰረተ ድምዳሜ ነው፡፡ አያችሁ… ገና ያልተነገረ ውጤት ቢኖርም ተቃዋሚዎች ያሸንፋሉ ተብሎ የተጠበቁባቸው ቦታዎች በሙሉ ገዢው ፓርቲ ጠቅሎ ወስዷቸዋል - በምርጫ ቦርድ መረጃ መሰረት፡፡ (ተቃዋሚዎች ግን ተጭበርብሯል እያሉ ነው!) ኢህአዴግ በዚህ ምርጫ “ለተማሪ ዜሮና መቶ አይሰጥም” የሚለውን የት/ቤት ትውፊታዊ አባባል ተገዳድሯል፡፡ (ተቃዋሚ 0፤ ኢህአዴግ 100? ነው ያገኙት)

እንዲያም ሆኖ ግን ብዙዎቻችን እንደምናስበው ኢህአዴግ ባገኘው ውጤት እምብዛም የተደሰተ አይመስልም፡፡ ባደረኩት ምልከታዊ ጥናት (ሳይንሳዊ አይደለም!) ገዢው ፓርቲ በውጤቱ ወይ አፍሯል ወይ ተፀፅቷል፡፡ እናንተ ግን ከእስከዛሬው የአውራው ፓርቲ ባህርይ ተነስታችሁ በዚህ ድምዳሜዬ ላትስማሙ ትችላለሁ፡፡ ግን ምን መሰላችሁ? ሁሌ ልጅነት የለም፡፡ ኢህአዴግ አሁን ጎልምሷል፡፡  (የግማሽ ክ/ዘመን  የስልጣን ልምድ አለው እኮ!)

እናላችሁ … በምርጫው 100 ከመቶ ማግኘቱ፣ በኢኮኖሚ ዘርፍ ያስመዘገበው የባለ ሁለት አሃዝ ዕድገት ውጤት መሆኑን አሳምሮ ቢያውቅም በተቃዋሚዎች ያለ ውጤት መቅረት ተፀፅቷል ወይም አፍሯል፡፡ እንደዚያ ባይሆንማ በዝረራ (Landslide) አሸንፈሃል ሲባል እንዴት አይቀውጠውም?  (በፌሽታ ማለቴ ነው!) እሱ ግን አላደረገውም - ቢያንስ እስካሁን፡፡ የሚገርመው ምን መሰላችሁ? ገዢው ፓርቲ በውጤቱ መፀፀቱን ወይም ማፈሩን ተቃዋሚዎችም ራሳቸው ገና አላወቁም፡፡ “ምርጫው ተጭበርብሯል” እያሉ እየወነጀሉት ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ ባለፈው ረቡዕ ውጤቱን ይፋ ሲያደርግ፣  የምርጫውን ድል በነጋታው ከግንቦት 20 ጋር ለማክበር ተመቸው ያሉም አልጠፉም ነበር፡፡   ግን ተሳስተዋል፡፡ እንኳን የምርጫው ድል፣ ግንቦት 20ም ራሱ እንደነገሩ ነው ያለፈው (ዝም ጭጭ ያለ በዓል ነበር!)

እንደወትሮው ቢሆን እኮ … EBC “የዘንድሮውን ግንቦት 20 ልዩ የሚያደርገው በምርጫው ማግስት በመዋሉ ነው” ሲለን ይከርም ነበር፡፡እናላችሁ …. እመኑኝ ኢህአዴግ በራሱ ውጤት ከተደሰተው በላይ በተቃዋሚዎች “ባዶ” መሆን አፍሯል ወይም ተፀፅቷል፡፡ ሳይናደድባቸውም አልቀረም፡፡ (ተቃዋሚ ባለበት አገር 100 በመቶ ማሸነፍ ተሰምቶ አይታወቅማ!) እነሰሜን ኮሪያና ሳዳም ሁሴን ነበሩ በዚህ ውጤት የሚታወቁት፡፡ አሁን ደግሞ ኢህአዴግ ሊሆን ነው፡፡ (በተቀሩት ቦታዎች ተቃዋሚዎች አንድ ሁለት መቀመጫ ቢያሸንፉ እኮ ይገላገል ነበር!) ግን ይሄውላችሁ… ተቃዋሚዎች ውጤት እንደሚያገኙ የሚያረጋግጥለት ቢያገኝ “ምርጫው ይደገም” ከማለት ሁሉ ወደኋላ የሚል አይመስለኝም!! (የምርጫ ቦርድ ምላሽ ባይታወቅም!) እርግጥ ነው ከምርጫው በፊት መረር ጠግነን ያለ (Aggressive) የምረጡኝ ቅስቀሳ አድርጓል፡፡ ያሰራቸው ቢል ቦርዶችና ፖስተሮች ብዛት፣ የቤት ለቤት ቅስቀሳው፣ የቡና ጠጡ ፕሮግራሙ፣ የEBC ዶክመንተሪ ፊልሞች… ከሁሉም በላይ ደግሞ የ1ለ5 ጥርነፋ ወዘተ … ኢህአዴግ በአገር ደረጃ ሳይሆን በአህጉር ደረጃ ለአፍሪካ የሚወዳደር ነበር ያስመሰለው፡፡ ፈርቶ ነበር ይላሉ - አንዳንዶች፡፡ (“አንዳንዴ ህዝብ አይታመንማ!”)

እንደሚመስለኝ ተቃዋሚዎች በቴሌቪዥን የፓርቲዎች ክርክር ላይ ትኩረት መሳባቸው ድንጋጤና ፍርሃት ሳይፈጥርበት አልቀረም፡፡ እናም አምርሮ ነበር፡፡ እልህ እንዳለበት ተማሪ ቀንና ሌሊት ምርጫው ላይ ቸክሎ አጠና፡፡ የማታ ማታ ኢህአዴግ - 100፤ ተቃዋሚዎች 0 ሆነ ውጤቱ! (አዲስ ሪከርድ እኮ ነው!) በመላው ዓለም እንኳንስ መቶ በመቶ … ከ50 በመቶ በላይ ማግኘት ብርቅ በሆነበት ዘመን ላይ እኮ ነው አውራው ፓርቲ ከ100 መቶ የደፈነው!! (በአሁኑ ወቅት በዓለም ብቸኛው ፓርቲ ሳይሆን አይቀርም!) እንዲህ ያለው ውጤት ደግሞ ከማሳጣትና ከአምባገነኖች ጐራ ከማሰለፍ ውጭ ምንም የሚፈይደው ነገር የለም፡፡ (መንግስት ለመሆን ይሄ ሁሉ ውጤት አያስፈልግም እኮ!!) እናም እመኑኝ … ኢህአዴግ የገዛ ራሱ ስኬት ሰለባ ሆኗል፡፡ (ማን ነበር “We are the victim of our own success” ያለው?)

ይኼውላችሁ … ምርጫ በመጣ ቁጥር እሱን ተከትሎ የሚከሰቱ ፖለቲካዊ ቀውሶችን ስመለከት፤ “ምርጫው ቢቀርብን ምን እናጣለን?” እያልኩ አበክሬ እቆዝማለሁ፡፡ (“ደፋር” እንዳትሉኝ!) የኒዮሊበራሊዝም አቀንቃኞቹ ሚዲያዎችና እነሂዩማን ራይትስዎች እንደሚሉት፤  9 የሚደርሱ ብሎገሮችና ጋዜጠኞች ወህኒ የወረዱት፣ 6 ገደማ መጽሔቶችና የሚዲያ ተቋማት የተከረቸሙት፣ 60 የሚደርሱ ጋዜጠኞች ከአገር የተሰደዱት እና ሌሎችም ውጥንቅጥጦች… ከፈረደበት ምርጫ ጋር ተያይዞ የመጣ ነው፡፡ (በምን ሂሳብ ይሄ ሁሉ አገራዊ ኪሳራ?)

የሚገርማችሁ ደግሞ በቅርቡ እንደተካሄደው የናይጄሪያ ምርጫ “ሰርፕራይዝ” ቢኖረው እንኳ ጥሩ ነበር፡፡ የጦቢያ ምርጫ ውጤት ግን ይታወቃል፡፡ እንኳን ተወላጆቹ የኒዮሊበራሊዝም አቀንቃኝ የሆኑት ሚዲያዎች ራሳቸው ገዢው ፓርቲ በዘንድሮ ምርጫ በዝረራ (Landside) እንደሚያሸንፍ የተናገሩት ከምርጫው በፊት ነው፡፡ ታዲያ የምን ልፋት ነው? በዚያ ላይ ለምርጫው የሚወጣው ወጪ ያሳዝናል (ብዙ ኮንዶሚኒየሞች አይሻሉንም!) ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ ምርጫው ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ያለው ጭንቀት!

እናላችሁ … ምርጫው ቢቀርስ እላለሁ!! ለምን መሰላችሁ? ኢህአዴግ ዝም ብሎ ከሥልጣን አይወርድም፡፡ አምባገነን ሆኖ እኮ አይደለም፡፡ ልማታዊ ስለሆነ ነው፡፡ በቃ የጦቢያን ህዝብ ባለመካከለኛ ገቢ የማድረግ ህልም አለው፡፡ (ከድህነት ካልተላቀቅን አይለቀንም!) እናላችሁ… ይሄን ይሄን ሳስብ ሁሌም  “ምርጫው ቢቀርብን ምን እናጣለን?” እላለሁ፡፡ የዲሞክራሲና የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ጠላት ሆኜ እንዳይመስላችሁ፡፡ ከዲሞክራሲ በፊት ዳቦ፣ ከምርጫ በፊት ልማት ብዬ ነው፡፡ አያችሁ … የምንበላውን መምረጥ ስንጀምር የሚገዛንንም ልንመርጥ እንችላለን፡፡ ያኔ የ1ለ5 አደረጃጀት፣ ኮንዶሚኒየም ቤቶች፣ ጥቃቅንና አነስተኛ ወዘተ… በምርጫው ላይ ተፅዕኖ አያመጡም፡፡ (ባለመካከለኛ ገቢ ሆነናላ!)

በነገራችን ላይ መንግስት በ97 ምርጫ የአውሮፓ ታዛቢ ቡድን አባል በነበረችው አና ጐሜዝ የተነሳ ዓለምአቀፍ የምርጫ ታዛቢዎችን “ዓይናችሁን ለአፈር” ማለቱ ተገቢ አይደለም (ነገር አካበደ እኮ!) የአፍሪካ ህብረት ታዛቢ ቡድን ሰሞኑን ባወጣው የመጀመሪያ ሪፖርቱ ላይ፤ በየጣቢያው በርካታ የህዝብ ታዛቢዎችን መመልከቱን ጠቁሞ ለምርጫው ግልጽነት እንዲሁም በሂደቱ እምነት ለማሳደር የተለያዩ ዓለምአቀፍ ታዛቢዎች መገኘታቸው ወሳኝ ነገር መሆኑን ገልጿል፡፡ የአና ጐሜዝ ጦስ የአውሮፓ ህብረትን ብቻ አይደለም ፊት ያስነሳው፡፡ የአሜሪካ መንግስትም ዲፕሎማቶቹ ምርጫውን እንዳይታዘቡ መከልከላቸውን ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡

የጦቢያ መንግስት አጋር ምናምን አያውቅም እንዴ? (አቦ! ኢህአዴግ አንዳንዴ ያበዛዋል!) ግን እኮ ዓለም አቀፍ ታዛቢ ቡድን ቢኖር … ተቃዋሚዎች ምርጫ ተጭበረበረ፣ ኮሮጆ ተገለበጠ ወዘተ… ሲሉ…. ብቻ ተውት! የቅድሙ ሃሳቤ ይሻላል፡፡

ከምሬ ነው … ይሄ የምርጫ ነገር ቢቆየን ነው የሚሻለው፡፡ አንድያውን መካከለኛ ገቢ ላይ ስንደርስ ምርጫውን ብንጀምር ምን ይመስላችኋል? እስከዚያው ግን “ሁሉ ነገር ወደ ልማት!” የሚለውን መፈክር ጠበቅ ብናደርግ ይመረጣል፡፡

የሚገርማችሁ እኮ በአንድ በኩል ገዢው ፓርቲ፤ በዓለም አስገራሚ የሚባል የ100 ፐርሰንት ውጤት አግኝቶ ድሉን በአደባባይ ለማክበር እንኳ አልቻለም - በተቃዋሚዎች “ባዶ ውጤት” ተፀፅቶ፡፡

በሌላ በኩል ተቃዋሚዎች ውጤቱን አንቀበልም ብለዋል፡፡

ምርጫ ቦርድ ደግሞ “የተጭበረበረ ነገር የለም፤ መሰረተቢስ አሉባልታ ነው” ይላል፡፡ (ግን በምኔው መረመረው??) ቆይ አሁን እውነት ማን ጋ ናት? ለእውነታ ዋጋ የሚሰጥ ባህል ሳንፈጥር እንከን የለሽ ምርጫ ለማካሄድ መሞከር ከንቱ ነው፡፡ ከምሬ ነው… ምርጫው ትንሽ ይቆየን!!

በነገራችን ላይ ተቃዋሚዎች በ97ቱ ምርጫ 147 መቀመጫዎችን አሸንፈው ነበር - ባይቀመጡበትም፡፡ በ2002 ምርጫ አንድ መቀመጫ ብቻ አሸነፉ፡፡ ዘንድሮ ደግሞ እንዳየነው ነው፡፡ (ኢህአዴግን ለፀፀትና ለሃፍረት የሚዳርግ ውጤት አስመዘገቡ!) ለማንኛውም ግን እንኳንም ምርጫው በሰላም ተጠናቀቀ፡፡

አንድ በዕድሜ የገፉ አዛውንት፤ ኢህአዴግ ምርጫውን ጠራርጐ ማሸነፉ ሲነገራቸው ምን አሉ መሰላችሁ?” “እናቴን ያገባ ሁሉም አባቴ ነው” (ኢህአዴግም ተቃዋሚም ለውጥ የለውም እያሉን ነው!) አሁን ምርጫው አልቋል፤ ወደኑሯችን እንመለስ!! (“አረረም መረረም ማበሬን ተወጣሁ” ነው ነገሩ!)

 

 

 

 

 

 

 

 

የዘመን መልክ ከዘመን ዘመን ይለያያል፡፡ አንዴ ፈክቶ አንዴ ፈዞ ይታያል፡፡ አንዳንዴ ዘመን ከዘመን ፍካትን ይበደራል፡፡ አንዳንዴ ዘመን ከዘመን ፍዘትን ይዋሳል፡፡ ፍካቱም ፍዘቱም፣ ድምቀቱም ጥቁረቱም … ከዘመን ዘመን ይናፀራል፡፡ ትላንት ምን ነበር?! ዛሬ ምንድን ነው? ነገስ ምን ይሆናል?! … ጥያቄዎቹ እነዚህና እነዚህ ናቸው፡፡እውነት ነው፤ ከመልስ ወይም ከትንታኔ፣ ጥያቄ ወይም ጥርጣሬ ይቀድማል፡፡ በዓለም ላይ … ከአንዱ ጥግ አንዱ ጥግ ዘመንን ተደግፈው የቆሙ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ሰው ከዘመን፣ ሰው ከእግዜር፣ እግዜር ከዘመን፤ ዘመንም ከዘመን ይቆራኛል፣ ይገናኛል፣ ይለያያል፡፡ የዘመን ቀለም አንዴ ደመቅ፣ አንዴ ፈዘዝ፣ አንዴ ነጣ፣ አንዴ ጠየም እያለ በሰው ልብ ላይ ይቀባል፡፡ አንዴ አምሮና ተውቦ፣ አንዴ ጠቁሮና አስጠልቶ በሰው ልብ ይሳላል፡፡

ስዕሉ ውብ ሊሆን ይችላል፡፡

ስዕሉ አስቀያሚ ሊሆን ይችላል፡፡

ግን ይሳላል፡፡ ዋናው ነገር መሳሉ ነው፡፡ ማማሩም ሆነ ማስጠላቱ ከመሳሉ ተከትሎ የሚመጣ ጉዳይ ነው፡፡

እርግጥ ነው፤ስዕሉ ውብ የሆነ’ለት ልቡ ጮቤ መርገጡ፣ነፍሱ እንጣጥ ማለትዋ እውነት ነው፡፡

 እርግጥ ነው፤ስዕሉ አስቀያሚ የሆነበት፣ ልቡ ስልል፣ ነፍሱ ዝልፍልፍ ማለትዋ እውነት ነው፡፡

ይህ የማይሻር እውነት፣ የማይካድ ሀቅ ነው፡፡

የሆኖ ሆኖ ዘመን የሚያነሳቸው ዘመን የሚጥላቸው፤ ዘመን የሚያነግሳቸው፣ ዘመን የሚሽራቸው ሰዎች አሉ፡፡ እውነቱን ለመናገር ዘመን ብቻውን ህልው አይደለም፡፡ በእርግጥ ሰው ኖረም፣ አልኖረም ፍጥረተ ዓለሙ፤ ወይም ዩኒቨርሱ መኖሩን መቀጠሉ አይቀርም፡፡

 አሁን የጠቀስኩት ዓረፍተ ነገር ግን እውነት ይሁን ውሸት መጣራት አለበት፡፡ ልክ ይሁን ስህተት መፈተን አለበት፡፡ እውነት ነው? … ፍጥረተ - ዓለም ‘ራሱን የቻለ ነው? … ከሰውም፣ ከፈጣሪውም የተገለለ ህልው ነው? ወይስ ከሰው ክህሎትም ሆነ ህላዌ የተፋታና ብቻውን የሚፀና እውነት ነው?! … ወይስ ምን?! …

መልስ ይሰጠናል ብላችሁ አትጠብቁ፡፡ መልስ የለኝም፡፡ ወይም ነገረ-ዓለሙን ባንድ ጆንያ ወደ ጫፉ በመቋጠር ገዢው እውነት ይህ ነው፤ ልላችሁ አልደፍርም፡፡

ዘመን ብቻውን ቋሚ ሊሆን ይችላል፡፡

ዘመን የሰው ጥገኛም ሊሆን ይችላል፡፡

ከሁለቱ አማራጮች የመጀመሪያው ሀሳብ የተሻለ እውነት ይመስላል፡፡ ግን ደግሞ ሰው ከሌለበት ዘመን ምን ጣዕም አለው?! … ዘመንን ዘመን የሚያሰኘው፣ ሰርቶ ሀብት የሚያካብትበት፤ ወልዶ የሚስምበት፣ ዘርቶ የሚቅምበት---ሰው ሲኖር አይደለም?! … ከሰው ኑሮና ግንዛቤ፣ ከሰው ትኩረትና ትንታኔ የተለየ ዘመን ዘመን ተብሎ ሊጠራ ይችላል?!

ጥያቄው ብዙ ነው፡፡

ስለ ጊዜና ስለ ዘመን ብዙ ገጣሚያን ተቀኝተዋል፤ብዙ ፀሐፍት አንቀፅ በአንቀፅ የተሰማቸውን ብለዋል፡፡

ስለ ዘመን ከተፃፉ ግጥሞች በጌታቸው በለጠ የተፃፈውን ቀጣዩን ግጥም እንይ፡-

ዘመኔን በችሎት

ዘመኑን ሰደብኩት፣

ድብን በል ብዬ፣

ሰደብኩት እንዲበግን፣

አፈር ብላ ብዬ፣

ገተርኩት ችሎት ፊት፣

አቅሙን ይወቅ ብዬ፡፡

እሱም ዘመን ሆኖ፣

የዘመን ኦቦላ፣

አሳር ያበላኛል፣

በነጋ በጠባ፡፡

እንባዬ ደረቀ፣

ዛሬስ ጀግና ሆኗል፣

ለካስ ሞት ራሱ፣

በልህ ይሸነፋል፡፡

አዋልኩት ሸንጎ ፊት

ዳኛ ይየው ብዬ፣

የተሸከምኩትን ዘባተሎ አዝዬ፡፡

የሚያስቡት አልሆን ሲል፣ የሚያልሙት አልሰምር ሲል፣ ከዘመን መላተም፣ ዘመንንም ማብጠልጠል አይቀርም፡፡ አይቀርም ሳይሆን የግድ ነው፡፡ 

ውሎ እንደ መፃጉ የሚያስጎነብስ፣ ያለ ቦታውና ያለ ጊዜው የደደረ፣ ተጨማሪ የሰውነት አካል አሸክሞ ለሁለት እጥፍ የሚያደርግ፤ ድካምን እንደ ስጋ አጉኖ እንደ መስጊድ ሚናር ከፍ አድርጎ ጀርባ ላይ የሚተክል  ሲሆን፣ ከዳር የተለያዩ የድህነት ዓይነቶችን እንደ ብርቅዬ እንስሳ እያስጎበኘ፤ በድህነት ፅናት፣ በእጦት ብርታት፣ በመከራ የሚያሽ ሲሆን፣ ኑሮ እንደ ሳነቴ ተራራ ለመውጣት አዳጋች፣ እንደ ሶፍዑመር ዋሻ ለመመላለስ አስቸጋሪ፣ አንዱ አክሱም ሐውልት ጫፍ ላይ ለመድረስ አድካሚ ሲሆን በአጭሩ ህይወት ዳገት ስትሆን ዘመን ላይ ጣት መቀሰር፣ ከዘመን መጋጨት፣ ከዘመን መጣላት፣ ዘመንን መሳደብ፣ ዘመንን መራገም ሊያጋጥም ይችላል፡፡

የጌታቸው በለጠ ግጥም እንዲህ ሲል ይቀጥላል፤

ያሸከመኝ አሳር፣

ቁልሉ አበዛዙ፣

አውርድልኝ ነበር

የጠቤ መዘዙ፡፡

ችሎት ፊት ያዋለኝ

ለፍትህ ያስጮኸኝ

የጫንቃዬ ሸክም፣

አላራምድ ያለኝ

እርሱ ነው ስቃዬ

ሰቅዞ የያዘኝ፡፡

ብሶቴን ጩኸቴን እሪታዬን፤

ሰምቶ፣

ሰምቶ አውጠንጥኖ

አውጠንጥኖ - ጥኖ፣

ዳኛው ፈረደብኝ

ይግባኝ መብቴን ገፎ

ዘመን አይከሰስ ዘመን አይደፈር

እንደለመድከው ኑር፣ ለዘመን ገብረህ፡፡

ሰው የዘመን ባሪያ ነው? ወይስ ዘመን የሰው አገልጋይ ነው? እውነቱ የቱ ነው?! እላይ የሰፈሩት ስንኞች ሰውን የዘመን ባሪያ የሚያደርጉ ይመስላሉ፡፡

 ዘመን አይከሰስ ዘመን አይደፈር

እንደለመድከው ኑር፣ ለዘመን ገብረህ፡፡

--- የሚሉት ሁለት ስንኞች ዘመንን ጌታ፣ ሰውን ባሪያ ያደርጋሉ፡፡ ማንም ቢሆን የሚያጎነብሰውና የሚገብረው የበላዩ ለሆነ አካል ነው፡፡

ንጉሱ ማን ነው? ዘመን ወይስ ሰው?

ዘመን ወይስ ሰው?!

“ደግ እሱስ ልቻለው.

ለምን ያህል ዘመን?

ኧረ ለመሆኑ ቁጥሩ ስንት ነው?

የዘመኑን ቀኑን ስሌቱን ልወቀው?

ብዬ ብጠይቀው ክቡር ፍርድ ቤቱን፣

“በእኛ አቆጣጠር ዘመን ጊዜ የለውም፣

እንዳስቻለህ ቻለው፣

የማይቻል የለም፣

ዘመን የሚረታው ዘመን ሊወለድ ነው፡፡

ለዘመን መወለድ

ያንተ ሞት ግድ ነው፡፡

ጣሩ ከበዛብህ፣

ሞትህን አፍጥነው፤

ፍትህ ዳኝነቱ ብይኑ ይሄው ነው፣

ዘመን ሞት አያውቅም ብይኑ ይሄው ነው፣

ይህ ግጥም ከሰወ ይልቅ፣ የዘመንን ህያውነት የሚያጎላ ነው፡፡ “ዘመን ሞት አያውቅም” ሲል የዘመንን ዘላለማዊነትለ “ቁርጥህን እወቀው” ሲል የሰውን ተረችነት የሚሰብክ ነው፡፡ ወይም ይመስላል ወይም …

ዘመን ከሰው ይበልጣል?!

ሰው ከዘመን ያንሳል?!

እርግጥ ነው፤ ዘመንን መልክ የሚያስይዘው ሰው ነው፡፡ ይህ እውነት ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይን የዚህ ግልባጭም እውነት ነው፡፡ ወይም ሊሆን ይችላል፡፡ ምንም ዘለግ ቢል፣ ምንም ወፈር ቢል፤ በዘመን ልክ የሚከረከም፣ በዘመን መጠን የሚሸነቅጥ ይኖራል፡፡

ዮሐንስ አድማሱ “የዘመኑ መንፈስ” በተሰኘ ግጥሙ ውስጥ እንዲህ የሚሉ ስንኞችን አስፍሯል፡፡

“ረቦ

ደብቢ

ሲያንዣብብ አንዳንዴ፣

የዘመኒ መንፈስ ያስፈራል ውበቱ፣

ሐኔ ሾተል ሆኗል ያልቻለው አፎቱ፣

ሥጋን አልፎ ነፍስን ይቆርጣል ስለቱ፡፡

በዚህ ግጥም ውስጥም የዘመን ኃያልነት ገኖና ደምቆ ይታያል፡፡ ዘመን (“የዘመኑ መንፈስ”) የማፈርሰውን ስጋውን ብቻ ሳይሆን የሚዘልመውን ነፍሱን ጭምር የሚቆርጥ ስለት እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ሰው ሟች ነው፤ ዘመን ግን ህያው ነው የሚል ይመስላል፡፡ እውነት ግን ዘመን አይሞትም?! …

ዝም ብዬ ሳስበው፣ አለ አይደል በቃ ዝም ብዬ ሳስበው፤ የሚሞትም ዘመን፣ የማይሞትም ዘመን ያለ ይመስለኛል፡፡ ሁሌ ተጠቃሽ ተስታዋሽ ዘመን የመኖሩን ያህል፣ መምድር ላይ የማቆያ ጊዜውን ጨርሶብዙም ሳይርቅ የሚረሳ ዘመንም አለ፡፡ ይሄ እውት ነው ወይም ይመስለኛል ወይም ….

ሰው ዘመንን ማስዋበና ገናና ማድረግ እንደሚችለው ሁሉ ዘመንም ሰውን ሊፈጥር ይችላል፡፡ አንዳድ ክስተቶችና አጋጣሚች ለዘመኑ አስፈላጊ የሆነ ሰውን የመፍጠር አቅም አላቸው፡፡ ታላላቅ ሰዎች እንዲሁ ዝም ብሎ ከተዘረጋው መስክ ወይም ማሳ ላይ እንደቅሎ አይዘገኑም፣ እንደቅጠል አይቀነጠሱም፡፡

እንደዚህ ዓይነት ሰዎችን በሆዱ የሚሰራቸው ችግር ነው፤ አምጦ የሚወልዳቸው ደግሞ ዘመን፡፡ የዓለምን ታሪክ ድምቀትና ፍካት የሚያጨልሙና የሚያኮሰምኑ ሂደቶች ወይም ክስተቶች የመኖራቸውን ያህል፤ በሚፈለጉበት ሰዓት ደርሰው መፍትሄ የሆኑ፤ በትክክለኛው ወቅት የተፈጠሩ ትክክለኛ ሰዎችም አሉ፡፡

እነዚህ ሰዎ ፈርጥ ሆነው የዓለም ታሪክን የሚያደምቁ፣ አልማዝ ሆነው የሰዎቹ ድርጊትም ሆነ ሰዎቹ እራሳቸው ውድ መሆናቸውን የሚመሰክሩ ናቸው፡፡በአሜሪካውያን የእርስ በርስ ጦርነት ጊዜ፤ ዘመኑ አብረሀም ሊንከን የመሰለ በሳልና ቆራጥ መሪ ባይፈጥር ኑሮ የአሜሪካ ታሪክ አሁን ከምናውቀው በተቃራኒው በሆነ፤ የጫለም ካርታ ላይ የሰፈረው መልከአ - ምድራዊ አቀማመጧም በተለየ ነበር፡፡ ያ የጦርነት ዘመን ሆቺ ሚኒን ባይፈጥር ኑሮ ዛሬ ቬትናም የምንላት ሀገር ሟች በሆነች፣ እንደ ሀገርም ባልቀጠለች ነበር፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ከዘመነ መሳፍንት ማህፀን ተወልደው በየቦታው ተበታተኑትን ግዛቶች ባይቆጠሩና መሪዎቹን ባያስገብሩ ኑሮ የዘመነ መሳፍንቱ እልቂት ባላከተመ ነበር፡፡ ሩህሩሁ መሪ አፄ ምኒልክ ኢትዮጵያን ባንድት አዋደው፣ ባንድ ንጉሥ ሥር እንድትተዳደር ባያደርጉ ኑሮ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ባልኖረች ነበር፡፡

እንደነበላይ ዘለቃ፣ ታከለ ወልደሐዋርያት፣ ጃጋማ ኪሎ፣ አበበ አረጋይ ወዘተ የመሳሰሉ አርበኞች በግራዚያኒ ክርን እንዲቆስም ብለው ጫካ ባይገቡና ባይታገሉ ኑሮ የኢትዮጵያ “በቀኝ ግዛት ያልተያዘች ብቸኛዋ ሀገር (ላይቤሪያን ሳይጨምር) ባልሆነች ነበር፡፡ ከዚህ በመነሳት ዘመን በየዘመኑ የ‘ራሱን ጀግና ይፈጥራል ማለት የሚቻል ይመስላል፡፡ ዘመኒ እንደልቡ አላጫውት ሲለው፣ ከመሸቱ ተቃርኖ ሲያገኘው፣ በመሰላቸትና በመታከለት ከዘመን ጋር ጠብ የሚፈጠር ሰውም ይኖራል፡፡ እነዚህን ሰዎች የሚወክለው የደበበ ሰይፉ ግጥም ነው፡፡

ደቤ በዛ በተባ ብዕሩ እንዲህ ይላል፡፡

“ለምን ሞተ ቢሉ

ንገሩ ለሁሉ

ሳትደብቁ ከቶ

ከዘመን ተኳርፋ

ከዘመን ተጣልቶ፡፡

“ከዘመን ከተጣሉት ጎራ አትመድበን፤ በዘመን ከነገሱት ጋር እንጂ!” በሚል ፀሎት እናሳርግ፡፡ 

 

 

 

 

 

Published in ህብረተሰብ
Saturday, 30 May 2015 12:01

ተውላጠ መክሊት

 

 

 

በአንዱ ባልደረባ ላፕቶፕ የጥላሁን ዘፈን ተከፍቶ እያዳመጥን አንድ ሃሳብ አናቴን ወጠወጠኝ፡፡

“ይኼ ዘፈን የጥላሁን ነው አይደል?” ስል በዙሪያዬ ያሉትን ጠየቅኳቸው፡፡

“አዎ ነው…” ካሉኝ በኋላ መልሰው “አይ የጥላሁንን አስመስሎ የዘፈነው…ማነው ስሙ” ብለው የአስመስሎ ዘፋኙን ስም ከኮርኒሱ ላይ ትንሽ ከፈለጉት በኋላ ሲያጡት “ያው የጥላሁን ነው” ብለው ጭጭ አሉ፡፡

አድቤ ሳደምጠው፤ ተመሳስሎ የተዘፈነው ከኦርጅናሌው ጋር የሚለያይበት ድምፅ የቱ ጋ እንደሆነ ማወቅ ተሳነኝ፡፡ በቃ ጥላሁን አይደለም፤ ግን ጥላሁን ነው፤ ብዬ ማድመጤን ቀጠልኩ፡፡  እያደመጥኩ የሃሳብ ሰንሰለቶች ተቀጣጥለው ይወጣጡብኝ ጀመር፡፡ “ታሪክ የሚፃፈው በአሸናፊዎች ነው” የምትል አባባል ከሃሳቤ ዜማ ጋር ምት ጠብቃ ታንቃጭልብኛለች፡፡

አዲሱ ዘፈን የጥንቱን ዘፈን አስረስቶ፣ የራሱን ባለጊዜነት ማረጋገጥ እንደሚችል እርግጠኛ ሆንኩኝ፡፡ አሮጌው ታሪክ በአዲሱ ይተካል፡፡ አሮጌው ዜማ በአዲሱ፡፡ ግን በአሮጌው እና በአዲሱ መሀል ምንም አዲስ ነገር ከሌለ… አዲሱ አሮጌውን ወርሶ ነው አዲስ የሆነው፡፡

ይኼንን እይታ ይዤ ወደማውቃቸው ወይንም ከዚህ በፊት ወደታዘብኳቸው ነገሮች ተመለከትኩ፡፡

መጀመሪያ ትዝ ያለኝ ስለ ገጣሚ በእውቀቱ ስዩም እና ስለ ተመሳሳዮቹ የተወራልኝ ጉዳይ ነው፡፡ “ተውላጠ” በእውቀቱ ልላቸው እችላለሁ፡፡ በፌስ ቡክ ማህበረሰብ ውስጥ እውነተኛው በእውቀቱን በስምም በአፃፃፍም ተመስለው ስራቸውን የሚያቀርቡ ሰዎች እንዳሉ ሰምቻለሁ፡፡

እውነተኛው ኦርጅናሉ ነው፡፡ ግን አርቴፊሻሉ የኦሪጅናሉን ስም እና ስራ ተመርኩዞ አዳዲስ እና ኦሪጅናል ግጥሞች መፍጠር ቢጀምር…እና ይጠጌውን ከይነኬው መለያየት ቢያቅትስ?

እንደዛማ እንዴት ይሆናል? ልክ መልካችን እና የጣታችን አሻራ የተለያየ እንደሆነው አስተሳሰብ እና ፈጠራችንም መጠነኛ ወይንም ከፍተኛ ልዩነት ሳይኖረው አይቀርም፡፡

ልዩነቱን ማወቅ አለመቻል ነው የአንዱን ታሪክ ለሌላው የሚያወርሰው፡፡

በሰማዩ ታሪክም ላይ የመውረስ ሙከራ ተደርጐ ነበር፡፡ ሰይጣን መላዕክቱን፤

“እኔ ነኝ እውነተኛው እግዚአብሔር” ብሎ አሻራ ለመውረስ ተፈራግጦ ነበር፡፡ አንድ የነበረው ቅዱስ ስብስብ ወደ ሁለት የተሰነጠቀው በዚህ መንስኤ ምክንያት ነው፡፡ ግን እግዚአብሔር አልፋ እና ኦሜጋ ስለሆነ ታሪኩንም ሆነ ማንነቱን መውረስ እንዲህ ቀላል አልሆነም፡፡

አዲሱ የአንድነት ፓርቲ የቀድሞውን ወርሶ፣ አንደኛው የሌላኛውን አጥፍቶ እንደፃፈው አይደለም የላይኛው ታሪክ፡፡ ግን ከዚያ ጊዜ እስካሁን ተመሳሳይ ድርጊት፣ ቅርፅ እና ይዘቱን እየለወጠ መወራረሱ ቀጥሏል፡፡

እንበልና፤ ከዛሬ አምስት መቶ አመት በኋላ… በአምስት መቶ የተለያዩ ድምፃዊ የጥላሁን ዜማ ቢዘፈን ማነው ኦርጅናል ማነው ቅጂ? ለማለት በጣም አዳጋች ነው የሚሆነው፡፡ “የጊዜ እንጂ የሰው ጀግና የለውም” በሚል እምነት የሚያመልክ ሁሉ በዘመኑ ያገኘውን ዘፈን ይወዳል፡፡ የወደደውን ደግሞ ከህይወቱ ጋር ያስተሳስራል፡፡ ህይወቱ እና መውደዱ ኦርጂናል ስላለመሆኑ ቢነገረው እንኳን አንቅሮ መትፋት አይችልም፡፡ አንቅሮ ተፍቶ የዛሬ አምስት መቶ አመት ወደ ኋላ ተመልሶ በትዝታ ለመኖር? አይመስልም፡፡

የአይሁድ ንጉስ ሰለሞን በአንድ ወቅት ገላውን ለመታጠብ የጣት ቀለበቱን አወለቀ፤ አሉ፡፡ የጣት ቀለበቱ የእሱን ማንነት የማወቂያ እና የማረጋገጫ ብቸኛው ማህተሙ ነው፡፡ እና  ገላውን ታጥቦ ሲጨርስ ሌላ ተራ ሰው የጣት ቀበለቱን አንስቶ አጥልቆታል፡፡ ያጠለቀው ተራ ሰው የንጉሥን ካባ ተደርቦለት ወደ ቤተመንግስቱ ገባ፡፡ ኦሪጅናሉ ንጉስ ስልጣኑንና ከሰማይ በታች ሁሉን የማድረግ አቅሙን ከቀለበቷ ጋር አጣ፡፡ ምናልባት፤ በዚህ ጊዜ ሳይሆን አይቀርም መጽሐፈ መክብብ እና የሰለሞን መዝሙር ተብለው የሚታወቁለትን ስራዎች ለመፍጠር የተገደደው፡፡ “ከሰማይ በታች ምንም አዲስ ነገር የለም…ንፋስን እንደመከተል ነው… አይንም ከማየት አይጠግብም ጆሮም ከመስማት አይሞላም… በአለም ያለ ሁሉም የከንቱ ከንቱ ነው” ለማለት የበቃው ምናልባት ከቀለበቱ መወረስ፣ ከመክኪሉቱ መነጠቅ በኋላ ሳይሆን  አይቀርም፤ ማን ያውቃል?

ቀለበቱ ሲመለስለት (እንዴት እንዳስመለሰ ባይነግሩኝም) በድጋሚ ስዩመ እግዚአብሔር ሆነ፡፡

እንግዲህ በዛች ቀለበቱ የተወከለው መክሊቱ ወይንም ኦሪጅናልነቱ ወይንም ከፈጣሪ የተሰጠው የስልጣን ቅቡልነት ሊሆን ይችላል፡፡ ገጣሚው በእውቀቱም ሆነ ድምፃዊው ጥላሁን ገሰሰ ይህ ቅባት አላቸው፡፡ የጥበብ ስራዎቻቸውን እንደ ሰለሞን የቀለበት ማህተም መመሰል እንችላለን፡፡ ግን የሰለሞንም ቀለበት በተመሳሳይ እንደተቀዳው ጥላሁን እና በእውቀቱም የሚቀዳቸው አያጡም፡፡ ቀጂው እውነተኛውን ተመሳስሎ የራሱን ተራ ማንነት በውዱ ይለውጣል፡፡ ሲቆለል የኖረ ስም፣ ዝና እና ታሪክን የራሱ ያደርጋል፡፡ የራሱ ለማድረግ ማሸነፍ መቻል አለበት፡፡ ጦርነቱ በጣም ጠላቱን በመምሰል እና ራሱን በመደበቅ ወይ በማስረሳት ችሎታው የሚወሰን ነው፡፡

የቀድሞውን የፖለቲካ ስርዓት እና ስርዓቱ ያቆማቸውን ታሪኮች መውረስ የሚቻለው… በድጋሚ ስርዓቱን በተመሳሳይ ድርጊት በመድገም ብቻ ነው፡፡ መድገም ወይንም መደጋገም መነሻውን ያስረሳል፡፡ በመጀመሪያው እና በተከታዮቹ መሀል ያለውን ልዩነት በተመሳሳይነት ውስጥ ያድበሰብሳል፡፡

የደራሲ በአሉ ግርማን ታሪክ ለመውረስ የሚፈልግ እንደ በአሉ ግርማ ይፅፋል፡፡ ይፅፍና “በዓሉ ግርማ አልሞተም” ወይንም “ከመሞቱ በፊት የሰራቸው ስራዎች” በሚል ስም መጽሐፍ ያሳትማል፡፡ ስኬታማም ይሆናል፡፡ ምክንያቱም የድሮው ታሪክ አዲሱን ዘመን የማስቆም አቅም የለውም፡፡ የድሮው ታሪክ በቆመበት ስፍራ ጥንት ላይ ነው ያለው፡፡ ከቆመበት የአላፊ ጊዜ ወደፊት የሚሻገረው ዝናው ብቻ ነው፡፡ በአዲሱ ዘመን የድሮውን ታሪክ መድገም የሚችል ባለ ጊዜ ግን ዝናውን የራሱ አድርጐ ይወርሳል፡፡ መውረስ ማለት ተወራሹን ደብዛውን አጥፍቶ በራስ መተካት ማለት ነው፡፡

በተሰጥኦ ውድድር ስም የተለያዩ ታዳጊዎች አምሳያ የሌላቸውን ሰዎች ለማስመሰል ሲሞክሩ ማየት የተለመደ ነው፡፡ አዲስ ማንነትን ከመፍጠር፣ ማንነት ያላቸውን መምሰል በቀላሉ (በአቋራጭ) ተቀባይነትን ያስገኝላቸዋል፡፡ ግን ደግነቱ፤ ሙሉ ለሙሉ ኦሪጅናሉን የመሆን አቅም ያለው አይገኝም፡፡ ቢገኝ እና የኦሪጅናሉን ስራ ከመድገም ወደ መፍጠር ቢሸጋገር፣ ኦሪጅናሉ አስመሳዩ ሆኖ አሮጌው በአዲሱ እንደሚረሳ ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡

በጊዜና በዘመን ላይ አካል ሳይሆን ሃሳብ ነው የሚነግሰው፡፡ ጥበብም በመሰረቱ ሃሳብ ነው፡፡ የፖለቲካ ስርዓትም ሃሳብ ነው፡፡ ታሪክ ከሀሳብ ድምር የተሸመነ ከጊዜ ውስጥ ራሱን በሰዎች መንፈስ አስገብቶ የሚላወስ ሃይል ነው፡፡ ሀይሉ፤ ሀገርን፣ ማህበረሰብን፣ ሃይማኖትን ይፈጥራል፡፡ ኃይሉ፤ የሰው ልጅን በስልጣኑ ስር የሚያደርግ ብቸኛው የፈጣሪ ተምሳሌት እና የመክሊት መግለጫ ነው፡፡ ይኼንን የሃይል ውክልና ለመሻማት መሞከር ተፈጥሯዊ ነገር ነው፡፡ ውክልና በተሰጥኦ የተቸራቸው ብቻ ግን አይደሉም ሃይሉን የሚፈልጉት፡፡

እግዜርን መሆን የሚችለው እግዜር ብቻ ቢሆንም፤ መሆን ያልቻለው ስልጣኑን ከመፈለግ ወደ ኋላ አስቀርቶት አያውቅም፡፡ ሰይጣን በእግዜር ስልጣን ላይ ለመቀመጥ ብቁ ባይሆንም ለመቀመጥ ከመሞከር ቦዝኖ እንደማይተወው እንደማለት፡፡

እንደ ሰይጣን እግዜርን በአንድ ጊዜ የሚወድ እና የሚጠላ ያለ አይመስለኝም፡፡ መውደዱ የሚያስታውቀው እግዜርን ለመሆን ከመሞከር ቦዝኖ አለማወቁ ላይ ነው፡፡ ጥላቻው ደግሞ የሚመነጨው ሊሆን እንደማይችል በማወቁ ይመስለኛል፡፡

ስልጣንን የማይፈልግ የለም፡፡ ስልጣን የሚገባውም የማይገባውም ይፈልገዋል፡፡ ጥበበኛም ህዝቡን የሚነቀንቅ ስልጣን ይጨብጣል፡፡ ከጨበጠው ለመንጠቅ አስመሳይ ይነሳል፤ ታሪኩን በዝና ስም ለመውረስ፡፡ ታሪክም ሆነ ዝና የስልጣን ዘውጐች ናቸው፡፡

በእውቀቱን ተመሳስለው የሚጽፉት ሰዎች እንደ በእውቀቱ ስራ የሚወዱት እና በዛው መጠን የሚጠሉት ነገር የለም፡፡ መውደዳቸው የሚታወቀው ማንነታቸውን በገጣሚው ማንነት ለመቀየር ምንም አለማንገራገራቸው ነው፡፡ መጥላታቸው የሚታወቀው የእሱን ማንነት አስረስተው በራሳቸው ማንነት ለመቀየር እና ታሪኩን በታሪካቸው (ቢሳካላቸው) ለመተካት አይናቸውን አለማሸታቸውን ልብ ስንል ነው፡፡

የማስመሰል ወይንም የመውረስ ፍላጐት ስልጣንን በተመለከቱ መስተጋብሮች ሁሉ ተመሳሳይ አካሄድ ያለው ይመስለኛል፡፡

ያ የፈረደበት “Animal Farm” የሚለው ድርሰት፣ ይሄንኑ እምነቴን ለማረጋገጥ በውስጤ በቂ ሆኖ ይደቀንብኛል፡፡

የእንስሶቹ ማህበር፣ ከሰው ልጆች ጭቆና ነፃ ለመውጣት መርጦ አመጽ ቀሰቀሰ፡፡ ሰይጣን መላዕክቶቹን በእግዜር ላይ ለማስነሳት በሞከረበት መንገድ ተመሳስሎ፡፡  አመፁ ተሳካ፤ እንስሳቱ ነፃ ወጡ፡፡ ነፃ ሲወጡ የሰው ልጅ እነሱን ለመጨቆን የሚገላገልባቸውን ኮተቶቹን ሁሉ ሰብስበው አስወገዱ፡፡ ሰውን ሰው ካደረጉት መገለጫዎቹ ማንኛውንም ነገሮች ልብሱን፣ መጠጡን የቁማር ሱሱን… የቤት ውስጥ ቁሳቁሶቹን፣ አልጋ እና የምርት መሳሪያዎቹን ላለመገልገል ምለው አስወገዱ፡፡ በታሪኩ ሂደት ውስጥ ግን የእንስሳቶቹ መሪዎች ቀስ በቀስ ሰውን ለመምሰል እየተፍጨረጨሩ መሆኑ ግልጽ ይሆን ጀመር፡፡ ከበፊቱ ለመለየት ሳይሆን የበፊቱን ለመምሰል እና ለመሆን ብቻ አመጽ እንደቀሰቀሱ ልብ ማለት እንችላለን፡፡

በስተመጨረሻ የምንረዳው ነገር እንስሳቶቹ ድሮውኑ (በደመነፍሳቸው ባያውቁትም) ሰውን መሆን እንዲችሉ ነው ሰውን ከመክሊቱ ያፈናቀሉት፡፡ ታሪኩንም ለመፋቅ የሞከሩት፡፡ እንስሳትን ነፃ ለማውጣት ሳይሆን የተመረጡ እንስሳት ሰው ሆነው ያልተመረጡት ላይ ስልጣን እንዲቀዳጁ ነው ያ ሁሉ ውጣ ውረድ፡፡ እንደ እንስሳት የሰውን ጭቆና የሚጠላ እና የሚወድ የለም፡፡ የሚወደው፤ እሱም ራሱ አንድ ቀን ጨቋኝ ለመሆን ምኞት ስላለው፤ የሚጠላው ደግሞ የመጨቆኛ ስልጣን በተፈጥሮው (በመክሊቱ) ስላልተቸረው ነው፡፡ ስለዚህ ወደ ማስመሰል ይገባል፡፡

መንግስትን አውርዶ በሌላ መንግስት የሚተካ አመፀኛ፤ ለመተካት የሚነሳው አዲስ ለውጥ ለማምጣት ሳይሆን ያወረደውን ቀዳሚውን ታሪክ ራሱ ወጥቶ ለመምሰል እንዲችል ነው፡፡ በኪናዊ ጥበብም ሆነ በህዝብ አስተዳደር ጥበብ፤ በመክሊት ያልተገኘ ውክልናን መክሊት ካላቸው በተመሳሳይ ካርቦን በመገልበጥ የስልጣን ባለቤት መሆን ይቻላል፡፡ ስለዚህ፤ ዜማውን እና ጊዜውን ይዞ የተገኘ ባለስልጣን ነው፡፡ ባለታሪክ ነው፡፡ ጊዜውን መያዝ የቻለ፤ እየወደደ መሆን ያቅተው ያቃተውን ቅናቱን… በማስመሰል ጥበብ፣ በተውላጠ መክሊት ወርሶ መሆን ይችላል፡፡  

 

 

 

Published in ህብረተሰብ
Saturday, 30 May 2015 11:59

የፀሐፍት ጥግ

(ስለገንዘብ)

የገንዘብ እጥረት የሃጢያት ሁሉ ሥር ነው፡፡

ማርክ ትዌይን

ብልህ ሰው ገንዘቡ በልቡ ውስጥ ሳይሆን በጭንቅላቱ ውስጥ ነው፡፡

ጆናታን ስዊፍት

ስግብግብነት የገንዘብ ጉዳይ አይደለም፤ የልብ ጉዳይ ነው፡፡

አንዲ ስታንሌይ

ሴቶች ባይኖሩ በዓለም ላይ ያለው ገንዘብ በሙሉ ትርጉም አይኖረውም ነበር፡፡

አሪስቶትል አናሲስ

ብዙ ገንዘብ ይዤ እንደ ምስኪን ድሃ መኖር እፈልጋለሁ፡፡

ፓብሎ ፒካሶ

ነፃ ምሣ የሚባል ነገር የለም፡፡

ሚልተን ፍሪድማን

ተበዳሪም አበዳሪም አትሁን፡፡

ዊሊያም ሼክስፒር

ገንዘብ መቆጠብ ስህተት ከሆነ ትክክል መሆን አልፈልግም፡፡

ዊሊያም ሻትነር

ገንዘብ ማለት ነፃነት ነው፡፡

ኬቪን ኦ‘ሊሪ

ገንዘብ ምርጥ ውሻ ሊገዛልህ ይችላል፤ ጭራውን እንዲቆላ የሚያደርገው ግን ፍቅር ብቻ ነው፡፡

ኪንኪ ፍሬድማን

ገንዘብ ገንዘብን እንደሚፈጥረው ሁሉ፣ ስኬትም ስኬትን ይፈጥራል፡፡

ኒኮላስ ቻምፎርት

ያለ ገንዘብ መኖር እችላለሁ፤ ያለ ፍቅር ግን መኖር አልችልም፡፡

ቤንጃሚን ፍራንክሊን

ለእያንዳንዱ ችግር ገንዘብ እንደ መፍትሄ ሲቆጠር ገንዘብ ራሱ ችግር ይሆናል፡፡

ሪቻርድ ኒድሃም

ገንዘብ ደስታን መግዛት አይችልም፤ ሊከራይ ግን ይችላል፡፡

ያልታወቀ ሰው

በገንዘብ ጉዳይ ሁሉም ሃይማኖቱ አንድ ነው።

ቮልቴር

ገንዘብ እንደ እጅ ወይም እንደ እግር ነው - ተጠቀምበት ወይም ጣለው፡፡

ሔነሪ ፎርድ

ሃሳብ የሁሉም ሃብቶች የመነሻ ነጥብ ነው፡፡

ናፖሊዮን ሂል

 

(ስለገንዘብ)

የገንዘብ እጥረት የሃጢያት ሁሉ ሥር ነው፡፡

ማርክ ትዌይን

ብልህ ሰው ገንዘቡ በልቡ ውስጥ ሳይሆን በጭንቅላቱ ውስጥ ነው፡፡

ጆናታን ስዊፍት

ስግብግብነት የገንዘብ ጉዳይ አይደለም፤ የልብ ጉዳይ ነው፡፡

አንዲ ስታንሌይ

ሴቶች ባይኖሩ በዓለም ላይ ያለው ገንዘብ በሙሉ ትርጉም አይኖረውም ነበር፡፡

አሪስቶትል አናሲስ

ብዙ ገንዘብ ይዤ እንደ ምስኪን ድሃ መኖር እፈልጋለሁ፡፡

ፓብሎ ፒካሶ

ነፃ ምሣ የሚባል ነገር የለም፡፡

ሚልተን ፍሪድማን

ተበዳሪም አበዳሪም አትሁን፡፡

ዊሊያም ሼክስፒር

ገንዘብ መቆጠብ ስህተት ከሆነ ትክክል መሆን አልፈልግም፡፡

ዊሊያም ሻትነር

ገንዘብ ማለት ነፃነት ነው፡፡

ኬቪን ኦ‘ሊሪ

ገንዘብ ምርጥ ውሻ ሊገዛልህ ይችላል፤ ጭራውን እንዲቆላ የሚያደርገው ግን ፍቅር ብቻ ነው፡፡

ኪንኪ ፍሬድማን

ገንዘብ ገንዘብን እንደሚፈጥረው ሁሉ፣ ስኬትም ስኬትን ይፈጥራል፡፡

ኒኮላስ ቻምፎርት

ያለ ገንዘብ መኖር እችላለሁ፤ ያለ ፍቅር ግን መኖር አልችልም፡፡

ቤንጃሚን ፍራንክሊን

ለእያንዳንዱ ችግር ገንዘብ እንደ መፍትሄ ሲቆጠር ገንዘብ ራሱ ችግር ይሆናል፡፡

ሪቻርድ ኒድሃም

ገንዘብ ደስታን መግዛት አይችልም፤ ሊከራይ ግን ይችላል፡፡

ያልታወቀ ሰው

በገንዘብ ጉዳይ ሁሉም ሃይማኖቱ አንድ ነው።

ቮልቴር

ገንዘብ እንደ እጅ ወይም እንደ እግር ነው - ተጠቀምበት ወይም ጣለው፡፡

ሔነሪ ፎርድ

ሃሳብ የሁሉም ሃብቶች የመነሻ ነጥብ ነው፡፡

ናፖሊዮን ሂል

 

Published in ጥበብ
Saturday, 30 May 2015 11:57

“ሰውስ ምን ይለኛል?”

 

 

 

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!

እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… “አንተ፣ እከሌ እኮ ሽበቱን ጥቁር ቀለም ግጥም አድርጎ ኑግ አያስመስለው መሰለህ!” ብለን ‘ጕድ’ የምንልበት ዘመን አለፈና አሁን፣ ‘ብሬስት፣’ አፍንጫ ምናምን ‘ሞዲፊክ’ የሚሠራበት ዘመን ደረስን አይደል! እኔ የምለው… ሙሉ ፊትን ‘ማሳመር’ ተጀመረ እንዴ! መጠየቅ አለብና… አንዳንድ ‘ኮመን’ የምንላቸው እንትናዬዎች በአንድ ጊዜ… “ደም ግባቷን አየህልኝ!” ምናምን የሚያስብል ‘ውበት’ ይይዙብን ጀምረዋላ!

ይቺን ስሙኝማ…ልጁ ለአባቱ “አባዬ ላገባ ነው…” ይለዋል፡ አባትም…

“ሸጋ፣  ሸጋ ነዋ! ለመሆኑ የምታገባት ምን አይነት ሴት ነች?” ይለዋል፡፡ ልጁም…

“አባዬ ቅር እንዳይልህ እንጂ የማገባት በዕድሜ የምትበልጠኝ ሴት ነች፡፡ የዘመኑ ወጣቶች ምንም አይመቹኝም፡፡ በዕድሜ ገፋ ያሉ ሴቶች የሚስብ ነገር አላቸው፡፡”

“ጥሩ፣ አንተን ደስ ካለህ ይሁን፡፡ ግን አንድ ነገር አለ…”

“ምን፣ አባዬ?”

“ነገ ተነገ ወዲያ ፊቷን ‘ማስተካከያ’ ለቀዶ ጥገና ገንዘብ አበድረኝ እንዳትለኝ!”

እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…በፊት እኮ አይደለም ጸጉር ማቅለም ምናምን ነገር ለየት ያለ ልብስ ለመልበስ እንኳን “ሰውስ ምን ይለኛል?” የጎረቤት ሀሜት ነው የሚዘለዝለኝ… ምናምን የሚባሉ ነገሮች ነበሩ፡፡ ዘንድሮ ‘ስልጣኔ’ እንዳለ ከእነተሳቢው ገባና…“ሰውስ ምን ይለኛል?” አይነት ነገር እየቀረ ነው፡፡

ግን እኮ… አለ አይደል… አንዳንዴ…“ሰውስ ምን ይለኛል?” ማለት ክፉ ነገር ላይሆን ይችላል፡፡ ገና ለገና… “በገዛ እንትኔ ማን ያገባዋል…” አይነት ነገር እየሆነ ህብረተሰቡን የሚያስቀይሙ፣ ከ‘አርአያነታቸው’ ይልቅ አፍራሽነታቸው የሚያመዝን ነገሮች ከማድረግ ሊጠበቀን ይችላል፡፡ ለምሳሌ ‘ሚኒስከርቷን’ና ‘ቦዲዋን’ ግጥም አድርጋ ማታ ለቅሶ ቤት ‘ለማስተዛዘን’ የምትሄድ እንትናዬ “በገዛ እንትኔ ማን ያገባዋል…” ብትል አሪፍ አይሆንም፡፡

ስሙኝማ…የሀዘን ነገር ካነሳን አይቀር… ብዙ ቦታ የሠልስት ስርአት መቅረቱ ጥሩ ነው፡፡ ሀዘንተኞቹ ከአላስፈላጊ መጉላላት ይተርፋሉ፣ ሰዉም ከመቸጋገር ያተርፈዋል፡ ግንላችሁ… ደግሞ ሠልስት መቅረቱ ብዙ እንትናዬዎች ውጪ የሚያድሩበትን ሰበብ አስቀርቶባቸዋል፡፡ ልክ ነዋ…“ሠልስት አዳር አለብኝ…” እየተባለ እንትን ሆቴል ክፍል ሠላሳ ሦስት ውስጥ የሚያድሩ እንትናዬዎች መአት ነበሯ! ቂ…ቂ…ቂ…

እናላችሁ… የጎረቤቱ እንትናዬ ላይ ቀልቡ የወደቀው እንትና ወደ ‘ስትራቴጂ ቀረጻ’ና ወደ ‘ተግባራዊ እርምጃ’ ከመግባቱ በፊት መጀመሪያ የሚመጣበት “ጎረቤትስ ምን ይላል?” አይነት ነገር ነበር፡፡ የኮተቤዎቹ እሱና እሷ ሸጎሌ የሚቃጠሩት እኮ… አለ አይደል… “መንደረተኛው አብረን ቢያየን ምን ይላል?” በሚል ነበር፡፡ (‘ነበር’ የሚለው ‘ኃላፊ ጊዜ’ ልብ ይባልልንማ! ቂ…ቂ…ቂ…

ዘንድሮማ ምን ችግር አለ! ከኮተቤ ሸጎሌ የለ… ከቦሌ ጉለሌ የለ…ከፒያሳ መካኒሳ የለ…ምን አለፋችሁ… እንዲህ ሁሉም ነገር ‘ግልጥ በግልጥ’ ሆኖ… ብቻ፣ ‘አገር አናት ላይ ምን እንደወጣ’ እሱ ይወቀው! ቂ…ቂ…ቂ…

ኮንዶሚኒየምን የመሰለ መብራት የሌለው ‘ሬድ ላይት ዲስትሪክት’ እያለ…ማንስ አየ አላየ ግድ ሊሰጠን ነው! እኔ የምለው…ይሄ የኮንዶሚኒየም ነገር…በቃ መኖሪያ ብቻ መሆኑ በሰርኩላር ምናምን ነገር ተሰረዘ እንዴ! አሀ…የምንሰማውና ወዳጆቻችን የሚነገሩን ነገር ሁሉ…የሆነ የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ‘ሶዶምና ገሞራ’ ምናምን የሆነ ይመስላል፡፡ ኮንዶሚኒየም የሚኖሩ ወላጆች ለሴት ልጆቻቸው በሰላም መውጣትና መግባት ቢጨነቁ አይገርምም! እናላችሁ… “ሰውስ ምን ይለኛል…” የማይባልበት ነገር ሆነና ‘ለመኖሪያነት’ እየተሠሩ ያሉት ኮንዶሚኒየሞች ኑሮን የሚያሳጥሩ ነገሮች እየበዙባቸው ነው፡፡

እናላችሁ…እነኚህ ነገሮች ሁሉ የበዙብን… አለ አይደል…ስልጣኔ እየተባለ ነው፡፡ (ለ‘ፖርኖው’ና ለምናምኑ ‘ሽግግር’ የምንጨነቀውን አንድ አሥረኛ ለቴክኖሎጂና እውቀት ሽግግር ብንጨነቅ ይሄኔ የት በደረስን!)

ስሙኝማ…ድሮ በ‘ሪቮዎች’ ምናምን ዘመን… አለ አይደል… “በኢምፔያሊስት ባህል በከሉን…” እየተባለ… አለ አይደል… “ያንኪ ጎ ሆም!” ይባል ነበር፡፡ ልጄ፣ ዘንድሮ… “ጎ ሆም…” ምናምን ብሎ ነገር የለም፡፡ መፈክር አስጽፈን አደባባይ አንውጣ እንጂ…“ያንኪ ካም ሆም!” የምንል ነው የሚመስለው፡፡ ብቻ በየምኗና በየምናምኗ ያየናትን ነገር ለቀም አድርገን ‘አዳብረን’ና ‘አገሪኛ ቀለም ሰጥተን’ (ቂ…ቂ…ቂ…) ጣራ እናደርሳታለን፡፡ እናላችሁ… ዘንድሮ በተለይ በ‘እነሆ በረከት’ ጉዳይ “ሰው ምን ይለኛል!” ምናምን ብሎ ነገር የለም፡፡

ስሙኝማ…እግረ መንገዴን የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ፡፡ ጥያቄ አለን… ያሁኖቹ ወዳጆቻችን ‘ያስቀየሙን’ ጊዜ “ጃኪ ቻን ጎ ሆም!” ልንል ነው? ቂ…ቂ…ቂ… ልክ ነዋ…በኋላ መፈክርም ለመጻፍ ካሁኑ ብናውቀው አሪፍ ነው፡፡ 

“ምን አለ በሉኝ ከጥቂት ዓመታት በኋላ የአባቶቻቸው ማንነት የሚያከራክሩ ልጆች ባይበዙ…” ያልከን ወዳጃችን…እውነት ብለሀል፡፡ አዝማሚያው ምንም ደስ የሚል ነገር የለበትም፡፡ የአባትነት ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…

ሆሊዉድ ውስጥ ነው አሉ፡፡ እናማ… ልጅየው ትምህርት ቤት ውስጥ እየበጠበጠ ያስቸግራል፡፡ ርዕሰ መምህሩም ያስጠራውና፤ 

“በሚቀጥለው ወር እናትህ ትምህርት ቤት እንድትመጣ ንገራት፣” ይለዋል፡፡ ልጅዬውም…

“ለእናቴ መንገር አልችልም፡፣” ሲል ይመልሳል፡፡ ርዕሰ መምህሩም…

“ማለት እናትህ የሚቀጥለው ወር የት እንደምትሆን አታውቅም ማለት ነው?” ብሎ ሲጠይቀው ልጁ ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው…

“አይ፣ በሚቀጥለው ወር አባቴ ማን እንደሚሆን አላውቅም፡፡”

አሪፍ አይደለች፡፡ እኛ ዘንድ እናት ለማምጣት የወር ቀጠሮ የሚሰጡ መኖራቸውን እንጃ እንጂ በሚቀጥለው ወር ‘ተባባሪ አባቱ’ (‘አሶሺዬት ፐሮፌሰር’ እንደማለት፡ ቂ…ቂ…ቂ…) ማን እንደሚሆን የማያውቅ መአት ልጅ ባይኖር ነው! ቂ…ቂ…ቂ… እናላችሁ…አንዳንድ ጊዜ ነገሩ ሁሉ ግራ፣ ግራ ሲሆንባችሁ፤ “ሰውስ ምን ይለኛል?” የሚሏት ነገር የሆነ መልካም ነገር ነበራት ትላላችሁ፡፡ ቢያንስ፣ ቢያንስ ድርጊቶች እኛ ደስ ስላለን ወይ ስላለን ሳይሆን ህብረተሰቡ ላይ ስለሚፈጥረው ነገርም እንጨነቅ ነበር፡፡ ለህብረተሰብ ማሰብ ደግሞ ለትውልድም ማሰብ ይሆናል፡፡ ስሙኝማ…አንዳንዷ እንትናዬ ዕድለኛ አይደለችም፡፡ ዶክተሩ የሚሠራበትን የአእምሮ በሽተኞች ሆስፒታል ለጓደኛው እያስጎበኘው ነው፡፡

“እዛ ጋ ያለው ሰውዬ ይታየሀል?” ሲል ዶክተሩ ይጠይቃል፡፡“አዎ፣ ይታየኛል፡፡ ምን ሆኖ ነው እዚህ የገባው?”

“የሠርጉ ዕለት ማታ ሙሽራው ክዳው ከሌላ ጋር ኮበለለችበት፡፡”

“አትለኝም! በጣም ያሳዝናል፡፡”

ጉብኝታቸውን ይቀጥላሉ፡፡ አንድ በብረት የታጠረ ክፍል ውስጥ ጭንቅላቱን ብረቱ ላይ በሀይል የሚደበድብ ሰው ያያሉ፡፡

“ያ ማን እንደሆነ ታውቃለህ?” ሲል ዶክተሩ ይጠይቃል፡፡“አላውቅም፣ ማነው እሱ?”

“እሱ ደግሞ የኮበለለችውን ሙሽራ ያገባው ነው፡፡”

አጅሪት…ሁለቱንም ፉዞ አድርጋቸው አረፈች! እኛ ዘንድ በመጡ…ሀያ ሁለቱን ‘ፉዞ’ ማድረግ የምትችል መአት አለች፡፡

ከዚች አይነቷ ሙሽራ ይሰውራችሁ፡፡

ስሙኝማ…አንድ ሰሞን የሠርጋቸው ዕለት ማታ ከሚዜ ጋር እነሆ በረከት ሲባባሉ የነበሩ ሙሽሮች እንዳሉ ይወራ ነበር፡፡ ነገርዬውማ ምን መሰላችሁ…ይሄ የሰው እንትናዬ እነሆ በረከት መባባል ከመብዛቱ የተነሳ አንድ ቤተ መጻሕፍት ሙሉ የሚወጣ ታሪክ አለ አሉ፡፡ እናማ… “ሰውስ ምን ይለኛል?” በአጉል ይሉኝታ መሥራት ያለብንን ነገሮች እንዳንሠራ ቢያግደንም አንዳንድ ጊዜ ደግሞ መሥራት የሌለብንን ነገሮች ከመሞከር ይከላከለን ነበር፡፡

ነገሮችን እያመዛዘንን የምንሠራበትን ዘመን ያቅርብልንማ!

ደህና ሰንብቱልኝማ!

 

 

 

 

Published in ባህል

 

 

 

(ሰማይ ከይንድይብ ረሐቐና፣ ምድሪ ከይንጥቐልል ገፊሑና)

 ከዕለታት አንድ ቀን በአንድ ሩቅ አገር የሚኖር አንድ ባለፀጋ ንጉሥ ነበር፡፡ 5 ልጆች አሉት፡፡ ዕድሜው ወደሞት እየተቃረበ ሲመጣ ዙፋኑን ለማን እንደሚሰጥ ግራ ይጋባል፡፡ በመጨረሻ ግን አምስቱንም ልጆቹን ይጠራና፤

“ውድ ልጆቼ! እነሆ ሰው ነኝና እንደንጉሥ ብኖርም እንደሰው መሞቻዬ ደረሰ፡፡ ከመካከላችሁ ለአንዳችሁ ዙፋነ -መንግሥቴን መስጠት የግድ አለብኝ፡፡ ለዚህ የመረጥኩት መንገድ እናንተን ማወዳደርና የተሻለ ውጤት ያመጣ ሥልጣነ - መንግሥቴን እንዲወርስና ሁላችሁንም በእኩል - ዐይን እያየ፣ ሳያዳላ፣ ሥርዓቱን ጠብቆ እንዲያስተዳድር፤ ሌሎቻችሁም ወንድማችሁን አንድም እንደወንድምነቱ፤ አንድም እንደመሪያችሁ አድርጋችሁ በቀና ዐይንና በፍቅር እያገዛችሁት እንድትተዳደሩና አገራችሁን እንድትጠብቁ ማድረግ ነው፡፡”

ልጆቹ በአባታቸው ማርጀትና መድከም ቢያዝኑም፤ ሌላ ምርጫ ስለሌላቸው፤

“የመወዳደሪያ ጥያቄው ምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁ፡፡

ንጉሡም፤

“እያንዳንዳችሁ፤ በየበኩላችሁ እስከዛሬ ደግ ሠርተናል የምትሉትን እጅግ ትልቅ ነገር አምጡና ንገሩኝ፡፡ የተሻለ ደግ ነገር የሰራውን ልጅ መርጬ እኔ ዳኝነት እሰጣለሁ፡፡ አሁን ሂዱና ነገ ከነግ - ወዲያ ተመለሱ” ብለው አሰናበታቸው፡፡

ልጆቹም ወደየክፍላቸው ሄዱ፡፡

በየፊናቸው ካሰቡበት  ከሁለት ሶስት ቀን በኋላ ሁሉም ወደአባታቸው ተመለሱ፡፡

ንጉሡም፤

“እህስ እጃችሁ ከምን? ምን ምን ደግ ሥራ ይዛችሁልኝ መጣችሁ?” ሲል ጠየቀ፡፡

የመጀመሪያው፣ የበኩር ልጃቸው፣

“ንጉሥ ሆይ፣ አንድ ቀን በሠፈራችን ከፍተኛ የቤት ቃጠሎ ደርሶ አይቼ አንዲት ልጃገረድ ቤት ውስጥ ልትቃጠል ስትል ለነብሴ ሳልሳሳ ገብቼ ተሸክሜ አውጥቼ አድኛታለሁ” አለ፡፡

ሁለተኛው ልጅ ቀጠለ:-

“ንጉሥ ሆይ፤ አንድ አዛውንት ዐይናቸው፣ በቅጡ የማያይ ናቸውና ገደል አፋፍ ላይ ተንጠልጥለው አይቼ፤ ሰው “ጉድ! ጉድ!” እያለ ሲተራመስ እኔ አፋፉን ወርጄ ከሥር ተሸክሜ አወጣሁዋቸው፡፡ ነብሳቸው ዳነ” አለ፡፡

ሶስተኛው ልጅ ደግሞ የሚከተለውን ተናገረ:-

“ንጉሥ ሆይ፤ እኔ ደግሞ አንድ ነብስ ያላወቀ ህፃን ከቤቱ ደጃፍ ካለ አውራ ጐዳና ላይ እየዳኸ ሲሄድ፤ ታኮ ያልተደረገለት ከባድ መኪና ወደኋላ እየተንሸራተተ መጥቶ ሊደፈጥጠው ሲል፣ ከሩቅ እየሮጥኩ ደርሼ ከጐማው ስር አፍሼ አውጥቼ አድኜዋለሁ”

አራተኛው ወንድምም፤

“ንጉሥ ሆይ፤ እኔም አንዲት አሮጊት መንገድ ላይ ወድቀው፣ የወደቁበት ድንጋይ ጭንቅላታቸውን መቷቸው ደም ሲፈሳቸው ደርሼ፤ ተሸክሜ ወደአቅራቢያው ጤና ጣቢያ ወስጄ አሳክሜ አድኛቸዋለሁ!” አለ፡፡

የመጨረሻው ወንድም እንዲህ አለ:-

“ንጉሥ ሆይ! እኔ ያደረግሁት ቀላል ነገር ነው፡፡

አንድ ቀን አንድ ከዚህ ቀደም በድሎኝ ተጣልተን፣ ተደባድበን የነበረ ሰው፤ ውሃ ውስጥ ገብቶ፣ እየሰመጠ ሳለ እኔ ደረስኩ፡፡ ሰውዬው “እባክህ በድዬሃለሁና ከመሞቴ በፊት ይቅርታ አድርግልኝ?” አለኝ፡፡ እኔም ወዲያው ልብሴን አወላልቄ ውሃው ውስጥ ገብቼ እየቀዘፍኩ በዋና ይዤው ወጣሁ - ዳነ!”

ንጉሡም፤

“ልጆቼ ሆይ! ሁላችሁም የፈፀማችሁት ወደር የሌለው መልካም ነገር ነው፡፡ የመጨረሻው ትንሹ ልጄ ግን ለበደለው ሰው ይቅርታ ማድረጉን፣ ያንንም በተግባር ማሳየቱን የሚያህል ትልቅ ነገር አይገኝም፡፡ እሱ መንግሥቴን ይውረስ፡፡ እናንተ ደግሞ ምንም ሳትመቀኙት የተለመደውን የደግነት እገዛችሁን ለግሱት!” ብለው ልጆቻቸውን አሰናበቱ፡፡

                                       ***

ይቅር - ባይነት የደግነት ሁሉ የበላይ ነው! ከእኔ ይቅር ማለት ታላቅ ፀጋ ነው፡፡ ብጐዳም እኔ ልለፈውና የጋራ ህልውናና ደህንነታችን፣ የጋራ ቤታችን በጠነከረ ሁኔታ ይቆይ ማለት፤ አርቆ አስተዋይነት ጭምር ነው፡፡ የመጨረሻ ትንሹ ልጅ ጠላቱን “እንዳሰመጠ ይቅር!” ማለት አቅቶት አይደለም! ለጠላቱ ሳይቀር ትምህርት ሊሰጥ የሚችል ልባዊ ደግነት ስላለው ነው! ይህን መቀዳጀት ወደፍፁም ፍቅር፣ ያለሂሳብ ወደሚሰጥ ፍቅር መጠጋት ነው! በአንፃሩ በስሌት የሚሰጥ ደግነትና ፍቅር፣ ዛሬ ይሄን ባደርግለት ነገ ይሄን ይከፍለኛል የሚባል ዓይነት ፍቅር ወይም ደግነት፤ ዞሮ ዞሮ ወደ ንግድ የሚገባ ነው! ዲሞክራሲም የዚህ ዓይነት ባህሪ አለው፡፡ ያለሂሳብ ስንሰራው ደግነት አለው፡፡ መስዋዕትነትን ይጠይቃል፡፡ በሚታሰብ ትከፍለኛለህ ሲባል ግን ዞሮ መግቢያው ንግድ ነው፡፡ ያ ንግድ ደግሞ በዋጋው የሚነገድ አይደለም፡፡ “ዋናውን ከመለሰልኝ ይበቃኛል” በሚል ተጀምሮ፤ “ባመጣሁበት ውሰደው” እየተባለ ሥንጥቅ ይተረፍበታል፡፡ ውሎ ሲያድር ደግሞ የተትረፈረፈ ጥቅም ለማግኘት ደባልቆ መሸጥ ይመጣል፡፡ ቅቤው ሙዝ ይገባበታል፣ የማሩ ጠጅ የስኳር ጠጅ ይሆናል፡፡ (በአራዳ ቋንቋ “የተወጋ” ነው ይባላል)

ከዚህም አልፎ የእኔን ሸቀጥ ብቻ ግዛ ወደማለት ይሸጋገራል - የተወጋም ቢሆን ዲሞክራሲም “የተወጋ ዲሞክራሲ” የሚሆንበት ሰዓት አለ፡፡ ለሠራነው ዲሞክራሲ ዋጋ ከመጠየቅ አልፈን “የተወጋም” ቢሆን፡፡ “የእኔን ዲሞክራሲ ብቻ ተቀበል” ማለት ይመጣል፡፡ (የእኔን ሸቀጥ ብቻ ግዛው ወደሚል ንግድ እንደመሸጋገር ማለት ነው) ውስጡ ቅድመ ሁኔታ እንደረድራለን - መመሪያ፣ ደንብ፣ ህግ፣ ዓለም አቀፍ የንግድ ውል እያልን፡፡ “ንፁህ የማር ጠጅ ነው” የሚል ማስታቂያ እንለጥፋለን እንደማለት ነው፡፡

ከዚያ ይህን ካልገዛህ ህልውና የለህም ወደማለት እናድጋለን፡፡ እጅ መጠምዘዝ እንጀምራለን የሚገርመው፤  ይህ ሁሉ የሚሆነው “ስለዲሞክራሲ” ሲባል ነው፡፡ ስለሰው ልጆች መብት ሲባል ነው! ያለንበት ዓለም ይህን እሳቤ ከፍ አድርጐ “ጐሎባላይዜሽን” ይለዋል፡፡ በዚህ እንፈራረማለን፡፡ የብድር ግዴታ እናስፈርማለን፡፡ የዚህ ሁሉ ውስጡ፣ የዚህ ሁሉ ቡጡ፣ የዚያው የተወጋ ዲሞክራሲ፣ የዚያው በልካችን የተሰፋ ዲሞክራሲ፤ “በነፃ መስፋፋት” ነው፡፡ የዚያው “የመልካም አስተዳደር” መስፈን ማንሰራፋት ነው፡፡ የዚያው “የፍትሕና እኩልነት” ዜማ “የተሻሻለ ቅንብር በእገሌ ሙዚቃ ቤት” እየተባለ መለፈፍ ነው፡፡ ከጥንታዊት ግሪክ ዲሞክራሲ እስከዛሬው “ዲሞክራሲ” የሄድንበት መንገድ “የንግድ ህግን” የተከተለ ነው፡፡ ለትርፍ የተቀነበበ በመሆኑ መቼም ቢሆን ሙስና አያጣውም! እርግጥ ሙስናው ዝማሬ - ቃናው፣ ቅኔ ዘረፋና አቋቋሙ፣ ይለያያል፡፡ እንደየአገሩ የውጪ ምንዛሬ መጠኑም ይለያያል፡፡ እንጂ ውስጠ ነገሩ አንድ ነው፡፡ “የናይጄሪያው ይከፋል፣ የኬንያው ትንሽ መለስ ያለ ነው፡፡ የኢትዮጵያው ጠየም ይላል፡፡ የሱዳኑ በጣም አልለየለትም ወዘተ” እንበል እንጂ ሙስና ሙስና ነው!! ሁሉም በዲሞክራሲ ስም፣ ሁሉም በሠፊው ህዝብ ስም፣ ሁሉም በፍትሐዊነት ስም፣ ሁሉም በነፃና አድልዎ - አልባ ምርጫ ስም፣ ሁሉም ቡድን በሰላም ስም የሚፈፅመው ምዝበራ ነው፡፡ ግለሰብ ሠራው፣ ቡድን ሠራው፣ ፓርቲ ሠራው፣ መንግሥት ሠራው አያጨቃጭቅም፡፡ የሙስና ቦቃ የለውም፡፡ ስለዲሞክራሲ ስናወራም የአሜሪካ ተፅዕኖ፣ የእንግሊዝና የጀርመን ተፅዕኖ ያመጣው ወዘተ ማለትም አያዋጣም፡፡ ዞሮ ዞሮ “ለአምጪው እንዲከፈል ህግ ያስገድዳል” ይላልና መጽሐፉ! ሀገራችን ከላይ ካልነው የዲሞክራሲ ሂደት ውጪ አይደለችም፡፡ በእርግጥ የራሷ ንቅሳት፣ የራሷ ክትባት፣ የራሷ ዕትብት አላት፡፡ ውስጧ ስንገባ ጓዳ ጐድጓዳዋ ብዙ እንደመሆኑ ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊ፣ እና ማህበራዊ ጣጣ - ፈንጣጣዋ ያለ ነው፡፡ ኢኮኖሚያዊና ኢኮኖሚስቷ፣ ወርቁ ቢጠፋ ሚዛኑ አይጥፋ የሚባል ዓይነት ነው፡፡ ማህበራዊ ኑሮዋና ነዋሪዋ የባሰ አታምጣ የሚል ነው፡፡ ፖለቲካዋና ፖለቲከኛዋ “ሰማይ እንዳንወጣ ራቀብን፣ ምድርን እንዳንጠቀልል ሰፋብን” የሚል፤ ራስ ሳይኖረው ትራስ ፍለጋ የሚዞር ምሁር ነው!

ስለሆነም፤ ከፊሉ የሞተ ፈረስ ይጋልባል፤ ከፊሉ የሌለ ፈረስ አለኝ ይላል፣ ከፊሉ ያገኘውን ፈረስ ከመጋለብ ይልቅ አፉን ይዞ ይጐትታል፡፡ ደግሞ ከፊሉ፣ መውደቁን ረስቶ ፈረሱ ብቻውን እየሮጠ፤ አለሁ እየጋለብኩ ነው” ይላል፡፡ ከፊሉ ሲመቸው የሚጋልብ ሳይመቸው የሚተኛ ነው፡፡ ከፊሉ ደግሞ ከፈረሱ ይልቅ ራሱ ያልተገራ ሆኖ ይደነባበራል፡፡ አንዳንዴ ጋላቢው ፈረሱ፤ ተጋላቢው ባለፈረሱ ይሆናል፡፡ ብዙ ዘመን ጋልቤያለሁ የሚለው ደግሞ ራሱም ማርጀቱን፣ ፈረሱም መገጣጠቡንና ማነከሱን፣ ማለክለኩንና አረፋ መድፈቁን ሳያስተውል “መጭ!” ይለዋል፡፡ ከዚህ ሁሉ ይሰውረን! የተሻለ ቀን እንመኝ!

 

 

 

Published in ርዕሰ አንቀፅ

 

 

 

  • ዶ/ር ነጋሶ የህገመንግስት ማሻሻያ ያስፈልጋል ብለዋል
  • አቶ ሙሼ፤ ኢህአዴግ ያገኘው ድምፅ የስነልቦና ጫና ውጤት ነው ይላሉ

     በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ የማስተርስ ዲግሪ ተማሪ የሆነው አቤል አየናቸው፤ ኢህአዴግ በዘንድሮ ምርጫ እንደሚያሸንፍ ጥርጣሬ አልነበረውም፡፡ ነገር ግን ሙሉ በሙሉ ይጠቀልለዋል የሚል ግምት እንዳልነበረው ይናገራል፡፡ “ቢያንስ 20 እና 25 የሚሆኑ የፓርላማ ወንበሮች በተቃዋሚዎች ይያዛሉ የሚል ግምት ነበረኝ” ብሏል አቤል፡፡

በተለይ ሰማያዊ ፓርቲ፣ መድረክና ኢዴፓ በፓርቲዎች ክርክር ወቅት ባሳዩት ጥንካሬ ብዙ ትኩረትና ድጋፍ መሳባቸውን የሚናገረው አስተያየት ሰጪው፤ ከዚህም በመነሳት በርከት ያሉ እጩዎቻቸው የፓርላማ ወንበር ያገኛሉ የሚል ግምት እንደነበረው ተናግሯል፡፡

“ተቃዋሚዎች ሙሉ ለሙሉ ወንበር ማጣታቸው በምርጫው አሳታፊነትና ተአማኒነት ላይ ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም” ብሏል አቤል፡፡ለቀጣይ 5 ዓመት የምናየው ፓርላማ አንድ አይነት ድምፅ የሚስተጋባበት መሆኑ ከፍተኛ ጉዳት እንዳለው የገለፀው አስተያየት ሰጪው፤ “ፓርላማው በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን ችግር የማስተጋባት አቅም አይኖረውም” የሚል ስጋት እንዳለው ይናገራል፡፡የለየለት አምባገነናዊ ስርአትን የሚከተሉ ሃገራት እንኳ በዚህ ደረጃ የምርጫ ውጤት አያስመዘግቡም ያለው አቤል፤ ኢህአዴግ ሁሉንም ጠቅልሎ ለመያዝ የሚያደርገውን ጥረት ረገብ አድርጎና የአውራ ፓርቲ ስርአት ለዚህች ሃገር እንደማይበጅ ተገንዝቦ፣ ብዝሃነትን ሊያስተናግድ የሚችል የምርጫ ፉክክር መፍጠር ይኖርበታል ሲል መክሯል፡፡

የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን መምህር የሆኑት አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው የምርጫውን ውጤት እንደጠበቅሁት አላገኘሁትም ይላሉ፡፡ የዛሬ ሳምንት ኢህአዴግ ያሸንፋል የሚል ግምቴን በዚሁ ጋዜጣ ላይ የሰጠሁ ቢሆንም ተቃዋሚዎች በተለይ ሰማያዊ ፓርቲ ጥቂት የፓርላማ ወንበር እንደሚያገኙ ጠብቄ ነበር ያሉት መምህሩ፤ የተነገረው የምርጫ ውጤቱ ለአገሪቱ የዲሞክራሲ ሥርዓት የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ኢምንት ነው ብለዋል፡፡ ውጤቱ ህብረተሰቡ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅና የፈለጉትን አመለካከት የመያዝ መብትን ሳያስተውለው እየተነጠቀ መሆኑን ያሳያልም ባይ ናቸው፡፡

የምርጫው ሂደት ላይ ጠንካራ ፉክክር አለመታየቱ፣ በተለይ ተቃዋሚዎች በሙሉ ልባቸው ወደ ምርጫው አለመግባታቸው ለዚህ አይነቱ ውጤት መመዝገብ አስተዋፅኦ ሳያበረክት አይቀርም ያሉት አስተያየት ሰጪው፤ ተቃዋሚዎች መራጮቻቸውን ሳያስመዘግቡ በምርጫው መሳተፋቸውና ገዥው ፓርቲ ይመርጡኛል ያላቸውን አስመዝግቦ ወይም እንዲመዘገቡ ቀስቅሶ በምርጫው መሳተፉ በውጤቱ ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል ብለዋል፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከዚህ በኋላ የምርጫ አካሄዳቸውን በሚገባ ማጤን ይኖርባቸዋል ይላሉ -መምህሩ፡፡ በዘንድሮ ምርጫ ጥሩ ውጤት ያስመዘገቡ ሰማያዊን የመሳሰሉ ፓርቲዎች በሚቀጥሉት 5 ዓመታት ጠንካራ ዝግጅት ካደረጉና የህዝብ አመኔታን ካተረፉ በቀጣዩ ምርጫ ሙሉ በሙሉ የማያሸንፉበት ምክንያት አይኖርም ብለዋል፡፡

ፓርቲዎች በምርጫ ቦርድ ገለልተኝነት ላይ ጥያቄ ካላቸው ምርጫ ሳይደርስ ከወዲሁ አንስተው ከገዥው ፓርቲ ጋር ለድርድር መቀመጥ አለባቸው ያሉት መምህሩ፤ ይህን ሳያደርጉ በምርጫ ወቅት በምርጫ ቦርድ ገለልተኝነት ላይ ጥያቄ ቢያነሱ ህብረተሰቡን ከማሰልቸት ያለፈ ለውጥ አያመጡም ሲሉም ሃሳባቸውን ገልፀዋል፡፡በ2002 በተደረገው ምርጫ መድረክን ወክለው የተወዳደሩትና ራሳቸውን ከፓርቲ ፖለቲካ ያገለሉት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በበኩላቸው፤ በዘንድሮ ምርጫ ብዙ አዳዲስ ነገሮች ማስተዋላቸውን ይናገራሉ - እንግዳ ያልሆነባቸው የኢህአዴግ ማሸነፍ ብቻ መሆኑን በመግለፅ፡፡የተፎካካሪ ፓርቲዎች ቁጥር መቀነስና የምርጫ ጣቢያዎች መብዛት አዳዲስ ነገሮች ከሚሏቸው ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡ የምርጫ ጣቢያዎች መብዛት አዎንታዊም አሉታዊም ጎን አለው ያሉት ዶ/ር ነጋሶ፤ በአዎንታዊ ጎኑ ህዝቡ በአቅራቢያው ያለእንግልት ቶሎ እንዲመርጥና ወደ ጉዳዩ እንዲሄድ ይረዳል፣ በአሉታዊ መልኩ ደግሞ 45ሺ ጣቢያዎች መኖራቸው የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ታዛቢ የማሰማራት አቅም ይፈታተናል ብለዋል፡፡ “ፓርቲዎች ወኪሎቻቸውን ሳያስቀምጡ የሚካሄድ ምርጫ ደግሞ አጠያያቂ ሊሆን ይችላል” ይላሉ፤ ዶ/ር ነጋሶ፡፡ በእርግጥም ተቃዋሚዎች በብዙ የምርጫ ጣቢያዎች ታዛቢዎች እንዳልነበሯቸው ዘገባዎች ይጠቁማሉ፡፡

የአፍሪካ ህብረት ታዛቢ ቡድን ስለምርጫው ያወጣውን ሪፖርትና በተለያዩ ሚዲያዎች የቀረቡ ዘገባዎችን መከታተላቸውን የጠቆሙት ዶ/ሩ፤ ቡድኑ በዘንድሮው ምርጫ ከቀድሞው የተሻለ ጠንካራ ሪፖርት ማቅረቡን መገንዘባቸውን ገልፀዋል፡፡

የአፍሪካ ህብረት ታዛቢ ቡድኑ በ356 የምርጫ ጣቢያዎች ብቻ ታዝቦ ያወጣው ሪፖርት በምርጫው ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ እንደሆነ የጠቀሱት ዶ/ር ነጋሶ፤ በምርጫ ጣቢያዎች የቅስቀሳ ፖስተሮች ተለጥፈው መገኘታቸው፣ የምርጫው እለት ቅስቀሳ ሲካሄድ ማየቱና ከታዘባቸው ጣቢያዎች 21.4 በመቶ በሚሆኑት ኮሮጆዎች ሳይፈተሹ ወደ ምርጫ መገባቱን መታዘቡ በቀላሉ የሚታይ አይሆንም ብለዋል፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ታዛቢዎች አለመኖርና የምርጫ ወረቀት እጥረት መከሰቱ በቡድኑ መጠቆሙም ምርጫው ጉድለቶች እንደነበሩበት ያሳያል ብለዋል - ዶ/ሩ፡፡በ1987 በተረቀቀው ህገ-መንግስት ላይ ጉልህ ተሳትፎ የነበራቸው ዶ/ር ነጋሶ፤ በኢትዮጵያ የሚከናወን ምርጫን በተመለከተ ህገ መንግስቱ ጭምር መሻሻል አለበት ይላሉ፡፡ የተመጣጣኝ ድምፅ አሰራር የሚተገበርበትን አካሄድ መከተል እንደሚሻል ጥናት ላይ የተመሰረተ ሃሳብ ማቅረባቸውን የጠቆሙት ምሁሩ፤ የተመጣጣኝ ድምፅ ስርአት ብንከተል የሀገራችንን ብዙሃነት በተገቢው ሁኔታ አሳታፊ አድርጎ ድምፅ ታፍኖ እንዳይቀር፣ ዜጎች ከማንኛውም ተሳትፎ እንዳይገለሉና ድምፃቸው ሙሉ ለሙሉ ዋጋ እንዲኖረው የሚያደርግ ስርአት ለመዘርጋት ያስችላል፤ ይህን ተግባራዊ ለማድረግም የህገ መንግስት ማሻሻያ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

መድረክ የምርጫውን ውጤት አልቀበልም ማለቱን እንደሰሙ የጠቆሙት ዶ/ር ነጋሶ፤ እንዲህ ያለ ችግር ሲያጋጥም ወደ ፍ/ቤት በማምራት ፋንታ ገለልተኛ አካል ይቋቋምና የምርጫው ውጤት ይጣራ ብሎ መጠየቁ ግራ እንዳጋባቸው ተናግረዋል፡፡የአለማቀፍ የህግ ባለሙያው ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያም  በበኩላቸው፤ “ምርጫውን ምርጫ ብዬ ስለማልቀበለው አስተያየት ለመስጠት እቸገራለሁ” ሲሉ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ 

የቀድሞው የኢዴፓ ፕሬዚዳንት አቶ ሙሼ ሰሙ፤ የምርጫው ውጤት እንደተገለፀው ሊሆን እንደሚችል ብዙ ጠቋሚ ነገሮች ነበሩ ሲሉ ያስታውሳሉ፡፡ ያለፉት 5 ምርጫዎች ከሂደት፣ ከዲሞክራሲ ባህሪና ከውጤት አኳያ ሲገመገሙ ብዙ ችግሮችና ምስቅልቅሎች የነበሩባቸው እንደሆኑ የጠቆሙት አቶ ሙሼ፤ በየጊዜው ምርጫ ተጭበርብሯል የሚለው የፓርቲዎች እሮሮ የሃሳብ ጥራት ወይም የችግሩን ምንጭ በጥናት ላይ ተመስርቶ ያለመፈተሽ ችግር ይታይበታል ይላሉ፡፡“ምርጫው ሲጀመር አንስቶ ድምፅ ሊጭበረበር ይችላል እየተባለ፣ ያንን ለማረም የሚያስችል ስራ ሳይሰሩ ወደ ምርጫ መግባት በራሱ ትርጉም የለውም” የሚሉት አቶ ሙሼ፤ ፓርቲዎች በአንድ በኩል በሂደቱ ላይ እምነት እንደሌላቸው እየተናገሩ፣ መሻሻል ሳይኖር ዝም ብለው በምርጫው መሳተፋቸው በራሱ አግባብ ነው ወይ ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡

ህዝብ ስለምርጫው ያለው አመለካከትና ፓርቲዎች በህብረተሰቡ ያላቸው ቅቡልነት አለመጠናቱም አንድ የምርጫ ሂደቱ ችግር ነው ይላሉ፤ አቶ ሙሼ፡፡ ገዥው ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚዎች ህዝቡ ከኔ ጋር ነው ሲሉ ይደመጣል የሚሉት የቀድሞው የተቃዋሚ አመራር፤ ነገር ግን ተቃዋሚዎችም ሆነ ገዥው ፓርቲ ምን ያህል የህብረተሰብ ክፍል ይደግፋቸዋል? የትኛው የህብረተሰብ አካልስ ተቀብሏቸዋል የሚለውን በጥናት ለማረጋገጥ አለመሞከሩ በኢትዮጵያ የሚካሄዱ ምርጫዎች ችግር ነው ባይ ናቸው፡፡ ፓርቲዎች በማህበረሰቡ ያላቸውን ቅቡልነት በጥናት ማረጋገጥና ለምርጫ ሲዘጋጁም ይሄን ያህል ህዝብ ሊመርጠን ይችላል፣ ይሄኛው ላይመርጠን ይችላል የሚለውን አስቀድመው ቢያውቁ እንደዘንድሮ አይነት የምርጫ ውጤት ሲያጋጥም መደናገጥ ላያጋጥም ይችላል ሲሉ አስረድተዋል፡፡በዘንድሮው ምርጫ የታዘቡትን ሲናገሩም፤ ምርጫውን የማጭበርበር ሂደቶች እንደ ምርጫ 97 ኮሮጆ በመቀየር፣ ካርድ በማሰራጨት ሳይሆን የስነ-ልቦና ጫናዎች ናቸው ይላሉ፡፡ ኢህአዴግ ያገኘው ውጤት የስነ - ልቦና ተፅዕኖ ድምፅ ነው የሚሉት አቶ ሙሼ፤ ማህበረሰቡ በሚሰጠው ድምፅ ኢህአዴግ ሲለወጥ ላለፉት 5 ምርጫዎች አለማየቱ፣ ተቃዋሚዎችን ቢመርጥ በስራ ቦታውና በማህበራዊ ህይወቱ የሚያጋጥመውን ተግዳሮት ሽሸት የስነ - ልቦና ተፅዕኖ ያሳድራል ይላሉ፡፡ ኢህአዴግን ወዶና ፈቅዶ የሚመርጥ የመኖሩን ያህል የሚደርስበትን ማህበራዊ ምስቅልቅል ሰግቶ ኢህአዴግን ሳይወድ የሚመርጥም አለ የሚሉት አቶ ሙሼ፤ ተቃዋሚን ብመርጥም ለውጥ አይመጣም ብሎ አስቀድሞ ማሰብም ሌላው የስነ - ልቦና ተፅዕኖ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡

“አርሶ አደሩ ተገዶ የምርጫ ካርድ እንዲወስድ መደረጉ ሳያንስ ተገዶ እንዲመርጥም ይደረጋል” የሚሉት አስተያየት ሰጪው፤ ወጣቱም ቢሆን ምርጫውን ተከትሎ ሊፈጠር የሚችልን እስርና እንግልት ስለማይፈልገው ድምፁን ለኢህአዴግ ሊሰጥ ይችላል ብለዋል፡፡

በቀጣይ ተቃዋሚዎች ምርጫው በደፈናው ተጭበረበረ ከማለት ይልቅ የችግሮቹን ስረ መሰረት የሚፈትሹ ጥናቶችን ሰርተው የሚያገኙትን የጥናት ውጤት እንደ ግብአት በመጠቀም ለእውነተኛ የፖለቲካ ትግል ራሳቸውን ሊያዘጋጁ ይገባል ብለዋል፡፡

የኢህአዴግ ጽ/ቤት የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ደስታ ተስፋው በበኩላቸው፤ “ህብረተሰቡ በድጋሚ ለኢህአዴግ ሙሉ ለሙሉ ኃላፊነት መስጠቱን ከምርጫው ውጤት አረጋግጠናል” ይላሉ፡፡

ገና የሚቀር ውጤት ቢኖርም ኢህአዴግ ሙሉ ለሙሉ ምርጫውን ቢያሸንፍ እንኳ አንዳንድ ተቃዋሚዎች እንደሚሉት፣ የምርጫውን ዲሞክራሲያዊነት አይቀይረውም ያሉት አቶ ደስታ፤ “መራጮች የተሻለው አማራጭ ይሄ ነው ብለው በሙሉ ፈቃደኝነት ከመረጡ የግድ ተቃዋሚ መግባት አለበት ተብሎ ከህግ አግባብ ውጪ ይሰራ ማለት ነው?” ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ ዲሞክራሲ ማለት የህዝብ ውሳኔ ማለት ነው ያሉት ኃላፊው፤ ተቃዋሚዎች አይመሩኝም ብሎ ህዝቡ ከወሰነ ውሳኔው መከበር አለበት ብለዋል፡፡ እንዲያም ሆኖ አንዳንድ ተቃዋሚዎች ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነው፣ በርካታ ድምፅ ያገኙበት አጋጣሚም እንዳለ አቶ ደስታ በመጥቀስ፤ ምርጫው በሚገባ አሳታፊና በምቹ የመወዳደሪያ መድረክ የተካሄደ ነው ብለዋል፡፡ 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

Page 3 of 19