Saturday, 16 May 2015 10:51

‘የመገላበጥ’ ነገር…

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…እኔ የምለው፣ ለሌላው ‘ምክር’ መስጠት ይህን ያህል የሚቀለን እንዴት ነው! አብዛኞቻችን የራሳችን ጉድ ‘ጓዳ’ ሆኖ…ለሌላው ምክር ሰጪዎች ሆነናል፡፡
እናላችሁ…የሆነ የምታወቁት ሰው አለ፡፡ እናላችሁ…ሲያያችሁ ሁልጊዜ ያው ናችሁ፡፡ የሆነ ንግርት ምናምን ያለባችሁ ይመስል ለሚሌኒየም የገዛችኋት ጫማ ቀለም አልቀበል ከማለቷ ሌላ…አሁንም እግራችሁ ላይ ነች፡ ታዲያላችሁ…ምን ይላችኋል…
“ስማ ብር ያለው አብሮ አደግ ጓደኛ ወይ ዘመድ የለህም?”
“ቢኖረኝስ!” ‘ቢኖረኝስ’ እንጂ ሌላ ምን ይባላል!
“አንድ ሁለት ሚሊዮን ስጠኝ በለውና የሆነች ኢንተርኔት ካፌ ነገር ክፈታ!” ይላችኋል፡፡ ወዳጆቼ ይሄ እናንተን አይመለከትም፡፡ ልክ ነዋ… እንኳን የምትሰጡት አንድና ሁለት ሚሊዮን ሊኖራችሁ ሚሊዮን የሚለውን ቁጥር የጻፋችሁት ስምንተኛ ክፍል ሚኒስትሪ ላይ ‘የናይጄሪያ ህዝብ ቁጥር ስንት ነው?’ ለሚለው ጥያቄ መልስ ስትሰጡ ነው። ቂ…ቂ…ቂ…
ደግሞ ሌላኛው ምን ይላችኋል…
“ስሚ ኤን.ጂ.ኦ. የምታውቂው ሰው የለሽም?”
“የማውቀው ሰው ቢኖርስ!” ‘ቢኖርስ’ እንጂ ሌላ ምን ይባላል!
“በቃ አንዱ ኤን.ጂ.ኦ. ሁለት ዓመት ብትሠሪ እኮ እኔ ነኝ ያለ ጂ ፕላስ ዋን ትሠሪ ነበር፡፡ ዘላለምሽን አሮጌ ሻንጣ ይዘሽ ሰፈር ለሰፈር ከምትዞሪ እወቂበት።”
እናላችሁ…አስቸጋሪ ነው፡፡ በእርግጥ ብዙ ሰው ለእናንተ በጎ ከማሰብ ይሆናል፡፡
“ምነው ጠፋህ?”
“ኧረ አልጠፋሁም፡፡”
“ጭራሽ አትታይም እኮ…”
“አለሁ ባንገናኝ ነው፡፡” በሆዳችሁ “ልጥፋ አልጥፋ ምን አገባው!” ምናምን ትላላችሁ፡፡
“አሁንም እዛው ድሮ መሥሪያ ቤትህ ነህ!”  ይሄኔ ነገር መጣ ማለት ነው፡፡
“አዎ…”
“አይ ዶንት ቢሊቭ ኢት! ገልበጥ ገልበጥ በል እንጂ!” በሆዳችሁ የእናቴ አባቴ አምላክ…” ብላችሁ እርግማን ቢጤ ትጀምሩና ትተዉታላችሁ፡፡
የምር ግን… አለ አይደል… አሁን ያለችሁበት ቦታ ለመኖራችሁ ችግሮቹ የውጪ ሳይሆኑ የእናንተ እንደሆኑ ሲያስመስሉት ቀሺም ነው፡፡
ደግሞላችሁ…ኮሚኩ ነገር ተሳክቶለታል የምትባሉ አይነት ከሆናችሁ ያው ሰው ምን ይላል… “አጅሬው አንተማ ምን ታደርግ፤ ላይ ያሉት በሙሉ ዘመዶችህ ናቸው አሉ…” ምናምን ይላችኋል፡፡
ደግሞላችሁ…ሌላውን ‘ሰው እንደ መምከር’ ቀላል የሆነ ነገር ዓለም ላይ እንደሌለ በማመሳከሪያነት ሊቀርብ የሚችል አይነቱ ይመጣና…
“አንተ… አሁንም እዚህ አገር ነህ!”
“አዎ፣ ታዲያ የት ልሆንልህ ነው!”
“ወጣ በል እንጂ፣ ሰዉ ሁሉ አሜሪካ፣ አውስትራሊያ እያለ ዶላሩን ሲሰበስብ አንተ ከአገር እንዳትወጣ ተገዝተሀል እንዴ! ነው ወይስ አገሪቷ “አደራ በምድር በሰማይ…” ተብለህ የተሰጠችህ የስለት አገር አደረግሀት!”
ኮሚኩ ነገር እኮ ምን መሰላችሁ…ልክ እኮ ፓስፖርቱን አዘጋጅቶ የአንድ የአምስት ምዕራብ አገሮች ቪዛ አስመትቶ  “ይሄ ሰውዬ መጥቶ አይወስድም እንዴ?” ሲል የከረመ ነው የሚመስለው። እሱ ራሱ የፈረደባት አሜሪካ ለመሄድ ሲለፋ ጆርጅ ቡሽና ኦባማን አሳልፎ ሌላ ፕሬዚደንት እየጠበቀ ነው፡ ቂ…ቂ…ቂ…
እናላችሁ…አስቸጋሪ ነገር ነው፡፡ ብዙዎቻችን ያኛው ሰው የእኛን ያሀል ማሰቢያ ኩላሊት የሌለው እያስመሰልን ‘ምክር’ ብለን የምንሰጠው… በቃ፣ ቀሺም ነው፡፡ ደግሞላችሁ ዘንድሮ በተደጋጋሚ የሚሰማ ‘ምክር’ አለላችሁ፡፡
“አንተ ሰውዬ፣ ዘንድሮም ጠጋ አላልኩም እንዳትለኝ!”
“ወዴት ነው ጠጋ የምለው?”
“አንተ ሰውዬ!… ወዴት ነው ጠጋ የምለው ትለኛለህ! እኔ የምለው… መንግሥተ ሰማያት ለአንተ ብቻ ቃል የተገባልህ ይመስል ሀቀኝነት አታብዛ!”
“ያልከኝ ሳይገባኝስ…ወዴት ነው የምጠጋው?”
“ወደ ጨረቃ እንድልህ ነው፡፡ ወደ ሰዎቹ ነዋ!  እነእንትና እኮ ቶዮታ ኤክስኪዩቲቭና ያሪስ የሚለዋውጡት ሎተሪ ደርሷቸው መሰለህ፡፡ የእኔ ጌታ አውቀውበት ጠጋ ስላሉ ነው፡፡”
እናላችሁ… ‘ሰዎቹ’ የሚለው ትርጉም የማያሻማ ቢሆንም (ቂ..ቂ..ቂ…) የመጠጋት ‘ስትራቴጂዎች’ ግልጽ ይደረጉልን! ‘ወደ ሰዎቹ ጠጋ የመባያ አንድ መቶ አንድ አስተማማኝ ዘዴዎች’ የሚል መጽሐፍ ይውጣልን፡፡ ሰውየው ‘ምክሩን ሲያጠናቅቅ’ ምን ይላል መሰላችሁ…
“ጌታው ዘንድሮ ወይ ጠጋ ትላለህ፣ ወይም ጥግ ላይ እንደተለጠፍክ ባቡሩ ያመልጥሀል…” ይላችኋል።
እናላችሁ…አንዳንድ ጊዜ የምክሮቹ አይነት ይቺዋ ያለችውን ‘አይ.ቂዋችንን’  ስለሚቀንሱብን አንዳንድ ሰዎችን በሩቅ ስናይ መንገድ ብንሻገር አይፈረድብንም። ‘ሲደብሩንስ!’
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የመደባበር ነገር ካሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ፡፡
እሱና እሷ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው የተገናኙት፣፣ እና እራት ይጋብዛታል፡፡ ግንላችሁ እራት እየተመገቡ… አለ አይደል… ትንሽ ደቂቃ አብረው እንደተቀመጡ ትደብረዋለች፡፡ (ወንዶች… “ጧት ከእንቅልፏ ስትነቃ እያት…” እንደሚባባሉት ማለት ነው፡ ቂ…ቂ…ቂ…) እናማ… እንደምንም ብሎ ትቷት ለመሄድ ይፈልጋል። ቀደም ሲል ለጓደኛው “ለክፉ ለደጉም አይታወቅምና መሀል ላይ ደውልልኝ…” ብሎት ነበር፡፡ ጓደኛውም እንደተባለው ይደውልለታል፡ እሱዬው ሞባይሉ ላይ ትንሽ አዳመጠና “እውነትህን ነው!” ሲል ይጮሀል። “በቃ አሁን መጣሁ…” ይላል፡፡ ለእሷዬዋም “መሄድ አለብኝ፣ አያቴ ሞተች አሉ…” ይላታል፡፡  እሷ ምን ብትለው ጥሩ ነው… “ተመስገን፣ የእኔም አያት ልትሞት ትንሽ ደቂቃ ነበር የቀራት…!” እንዲህም አይነት መደባበርም አለ፡፡
እራት የምትጋበዙ እንትናዬዎች ሰውያችሁ ሞባይሉ ላይ… አለ አይደለ… “እውነትህን ነው!” ብሎ ከጮኸ አያቱ ሞተዋል ማለት ነው፡ ቂ…ቂ…ቂ…
ደግሞ ሌላ ‘መካሪ’ አለላችሁ..
“አንቺ አሁንም ከእሱ ጋር ነሽ?”
“ምነው፣ አሁንም ከእሱ ጋር ነሽ ማለት ምን ማለት ነው?”
“አሁንም መንግሥት መሥሪያ ቤት ምናምን ነው የሚሠራው?”
“አዎ፣ ችግር አለው እንዴ?”
“ያንቺ ነገር እኮ… የምትኖሪው ለነፍስ ነው እንዴ! ይሄን የመሰለ መልክ ይዘሽ ዘላለሙን ሞዴል ስድስት ምናምን እያለ ከሚሰለፍ ምስኪን ጋር ምን ያዳርቅሻል! የእኔ እመቤት ገልበጥ ብትይ ይሻልሻል፡፡ አለበለዛ ዓለም ላይሽ ላይ ትገለበጥብሻለች፡፡”
እና እነኚህ ‘ገልበጥ በል’ና ‘ገልበጥ በይ’ ነገሮች ግራ እያጋቡን ነው፡፡ እኔ የምለው…ገልበጥ ሲባል ‘ከአልጋ መውደቅ’ አለ አይደል እንዴ! ነው ወይስ ከ‘አልጋ መውደቅም’ አንዱ ገልበጥ መባያ መንገድ ነው!
ስሙኝማ…እግረ መንገዴን የሆነች ነገር ትዝ ብላኝ ነው፡፡ ትንሽ ትልቁ ከ‘አልጋ መውደቅ’ ለምዶበት ወደፊት ‘ኃጢአታችንን’ መናዘዝ የምንፈልግ ሰዎች በማህበር ተደራጅተን መምጣት የሚኖርብን ይመስለኛል፡፡ አሀ… እያንዳንዳችንን በተናጥል የሚያናዝዙ በቂ የኃይማኖት አባቶች አይኖሩማ! ሰው በጉዱ ስለማይስቅ አልሳቅሁም፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
ገልበጥ በል፣ ገልበጥ በይ የሚለው ምክር ለትንሽ ጊዜ በስምምነት ይታገድልንማ፡፡ አሀ…ልጄ ስንት ‘የሚያገላብጠን ነገር’ እያለ...
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Published in ባህል
Saturday, 16 May 2015 10:50

የስደት ስለት!

የእናት መጥፎና የስደት ጥሩ የለውም፡፡ ጥሩ ቢኖርም በጥቂቱ ነው፡፡ እሱም ከብዙ መከራና ስቃይ በኋላ የሚደረስበት ነው፡፡ ይህን ተራራ ውጣው፤ ይሄን ወንዝ ተሻገረው፤ ይሄን ዳገት ቧጠው፣ ይሄን ቁልቁለት ሩጠው፤ ይሄን ሜዳ ጋልበውን ወዘተ የተባልከውን ካደረግክ በኋላ የምትደርስበት ነጥብ ነው፡፡  
በተረፈ እንደ ጠል በረሃ ላይ ረግፈው፤ እንደ ጠጠር አሸዋ ላይ ወድቀው፤ እንደ ዝንጀሮ ከጫካ ጫካ ተንከራተው የሚጨብጡት ወይም ሊጨብጡ የሚመኙት ህልም መሳይ ነገር ነው፤ ስደት!
እውነት ነው፤ የስደት ጥሩ የለውም፡፡ ቁሳዊ ፍላጐትን ማሟላትና ከገቢ አንፃር ስኬትን ማስመዝገብ ቢቻልም፤ ይህ የተጣራ ደስታ የሚሰጥ ክስተት ሊሆን አይችልም፡፡ ሆድ ሲሞላ አዕምሮ ይራባል፡፡ ስጋ ሲደልብ መንፈስ ይታረዛል። አንዱን ሲይዙት አንዱ ያመልጣል፡፡ ዓለም እንዲህ ናት፡፡
የስደት ስለት ወደፊትም ሆነ ወደ ኋላ ሲመለስ እንደ መጋዝ ሁሉን ይቆርጣል፡፡ የተቆረጠ መድማቱ አይቀርም፡፡ የየትኛውም ሰው ደም ሲፈስ ይቆረቁራል፡፡ ደሙ ኢትዮጵያዊ ሲሆን ደግሞ ልብን ያሸብራል፡፡ ቅስም ይሰብራል፡፡ ቀልብ ይሰልባል፡፡ ሰላም ይነሳል፡፡ እንቅልፍ ያሳጣል፡፡ ምኞት ይከላል፡፡ ህልም ይቀላል፡፡
ብንችልና ስደት እስከ ዓለም ጥግ ብናሳድደው፤ ከነነፍሱ ገንዘን ብንቀብረው፤ ቀብረን አፈር ብናለብሰው፤ አፈር አልብሰን ድንጋይ ብንጭነው፤ እልል… ልልልል ማለት ዕጣችን በሆነ ነበር፡፡
ነገር ግን አልሆነም፡፡ ምኞታችንና እውነታው እስከመቼም ሊታረቁ የሚችሉ አይመስልም፡፡
ሰው ሰው በመሆኑ ብቻ ሊገጥሙት ከሚችሉት ነገሮች አንዱ ስደት ነው፡፡ በተፈጥሮም ሆነ ሰው ሰራሽ በሆነ ምክንያት መሰደድ ሊያጋጥም ይችላል፡፡ ሰዎች ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሱ፤ የብሱን እየተፈናጠሩ፤ ባህሩን እየተሻገሩ፤ ከሀገር ሀገር እየቀየሩ፤ በመስራት ኑሯቸውን ሊደጉሙና ህይወታቸውን ሊያቀኑ መለስ ቀለስ ሊሉ ይችላሉ። ይህ ህያው በመሆን ምክንያትና የተሻለ ነገር ለማግኘት ባለመ የዕለት በዕለት እንቅስቃሴ መነሻነት ሊያጋጥም የሚችል ነው፡፡
የስደት ስለት ለማንም አይራራም፡፡ ፊት የሰጠውን ሰው ሁሉ አንገት ይቀነጥሳል፡፡ ህያውን ወደሙትነት ይቀይራል፡፡ ብርቱውን ስጋውን ያጣምናል፡፡ ነፍሱን ያልማል፡፡ ደመነፍሱን ይንጣል፡፡ መንፈሱን ይድጣል፡፡
የስደት ስለት ዶልዱሞ አያውቅም፡፡ ሁሌም ስል ነው፡፡ ሞረዱ እጦት፤ ጉልበቱ ድህነት ነው። ትንሽ ኑሮው የደከመ ሰው ሁሉ ነፃ ነኝ ማለት የሚችል አይመስልም፡፡ ስደት ያሳድደዋል፡፡
በምኞት መላ ሰውነቱ ሰክሮ፣ በተስፋ ነፍሱ ይለመልምና ለመሰደድ ቆርጦ ይነሳል፡፡ ከስደት ጨርሰው የተመለሱትንም ሆነ ለዕረፍት የሚመጡትን በማየት መንፈሱ እረፍት ያጣል። በምኞት ይናጣል፡፡ እንደነሱ መናገር፤ እንደነሱ መልበስ፤ እንደነሱ ትልልቅ ሆቴሎች ገብቶ መመገብ፤ እንደነሱ በርከት ያለ ጉርሻ (ቲፕ) መስጠት ይፈልጋል፡፡ መታወቂያና ፓስፖርት ሳይዝ በተመቸው መንገድ ሀገሩን ለቆ ይርቃል። ህልሙን አቅፎ ይሮጣል፡፡ ከባይተዋርነት ኩሬ የሚበቃውን ይጠልቃል፡፡ ከመፃተኛነት ደሴት ሰብዕናውን ይነጥቃል፡፡ ከእንግልት እቅፍ ማንነቱን ይመዛል፡፡
ነቢዩ እያሱ “ስደት በጋዜጠኛው ዓይን” በሚል ርዕስ ባሳተመው መጽሐፍ ላይ የሚከተለውን ይላል፤
“በሱዳን በረሃዎች ከእባብና ከጊንጥ እየታገሉ፣ በኬንያ የስደተኞች ካምፖች በችግር እየተበሳጩና የባዕድ ፊት እየገረፋቸው፣ የአፍሪካን አህጉር በተገኘው መጓጓዣ ሲያቋርጡ በጉቦና በእስራት የተዋከቡ፣ ወዲያውን ሲሻገሩ በጀልባቸው መስጠም የአዞ እራት የሆኑ ዛሬም ስደትን የተሻለ አማራጭ አድርገው የቀጠሉ አያሌ ናቸው። ኢትዮጵያ ከአጐራባች አገሮች ሁሉ የተሻለ የተፈጥሮ ሃብትም፣ አገሩን የሚወድ ህዝብ ያላት ሆና ዜጐቿ ለስደት የመዳረጋቸው እንቆቅልሽ መሪዎች የፈጠሩት ፍትህ አልባ ማሽቆልቆል ነው።”
ያሳዝናል፡፡ በጣም ያሳዝናል፡፡ እጅግ በጣም ያሳዝናል፡፡
የአንቀፁን የመጨረሻ ዓ.ነገር መተንተን በሁለት አቅጣጫ የሚከወን ነው፡፡ አንደኛው በፖለቲካ አቋማቸው ምክንያት የሚሰደዱትን ሲያመለክት፣ ሁለተኛው መልካምና ፍትሀዊ የኢኮኖሚ ሁኔታ ባለመቻቸቱ ምክንያት የሚሰደዱትን ይጠቁማል፡፡ ሁለቱም በመንግሥት ደካማ አስተዳደር ምክንያት የሚከሰቱ መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡
ስደት ወይም ከትውልድ ሀገር መውጣት ከመንጋው እንደተለየ ጅብ ወይም አንበሳ የሚያቅበዘብዝ ሲሆን፤ እንደ አሳ ከለመደው ባህር ወጥቶ ምድረ በዳ ላይ የመጣልን ያህል ከባድ ነው።
የዶ/ር ፍቃደ አዘዘን “ውጭ አገር” የተሰኘ ግጥም እንመልከት፤
“ብቸኝነት ማለት
አንድ ክፍል አንድ ቤት፤
አራት ግርግዳ
እውስጧ ጠባብ አልጋ፤
አይምሰልህ ልጄ!
ነውና ብቸኛ የረገፈ ቅጠል፣
ከባህሉ ውጪ ከድንበሩ ኮለል፡፡
በዚህ ግጥም ስደተኛው “በረገፈ ቅጠል” ተመስሏል፡፡ እውነት ነው፤ መሰደድ ከለመዱትና የራስ ከሆነ ማንነት ርቆ በሰው ሀገር ከበቀለ ዛፍ ላይ የሚወድቅ ቅጠል መሆን ነው፡፡
በሊቢያ በረሀ በአይኤስ የታረዱት ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦች አብዛኞቹ ሳይነግሯቸውና ሳይሰናበቷቸው መሄዳቸውን ገልጸዋል፡፡
ይህም ቅር የሚል ሀሳብ መንጭቶ ከስደት ሀሳባቸው እንዳያሰናክላቸው ከማሰብ ነው፡፡ ያሰቡትን ለወላጆቻቸው ቢነግሩና ቤተሰቦቻቸውን ቢያማክሩ ሊገጥማቸው የሚችለውን ተቃውሞ በመስጋት ሳይሰበናቱ ለመሄድ ወስነዋል፡፡
ይሄ በአንድ ስነቃላችን ውስጥ ተጠቅልሎ ይገኛል፡፡ እነሆ፤
“አንበሳ ጋሜውን ቢያኩት ይደማል ወይ
የከፋው ሰው ሲሄድ ይሰናበታል ወይ”
ሌላኛው የስደት አስቀያሚ ገፅታ ይህ ነው። መመለስ እንደ መውጣት ቀላል አይደለም፡፡ መሄዱ አልጋ ባልጋ ባይሆንም መመለሱ ግን ፅንን ያለ ቀጋ ነው፡፡
“ምን ይዤ ልመለስ ወደ እናቴ ቤት” የሚለው ገለጻ እምቅ ስሜታቸውን የሚገልፅ፣ ስውር ሀሳባቸውን የሚያሳይ ነው፡፡
የኑረዲን ዒሳ “እመጣልሻለሁ” የተሰኘ ግጥም እንዲህ ይላል፡-
“ወርቅ ስትይኝ ወርቅ
ጨርቅ ስትይኝ ጨርቅ
አምባር ስትይ አምባር
አልቦም ስትይ አልቦ
ምን ያላኩት አለ
ምንድን ቅራቅንቦ
ላክ ያልሽኝን ሁሉ ስልክ ባጅቻለሁ
አሁንም ና ስትይ ቦርቄልሻለሁ
ደሞ አንቺ ብለሽኝ እንዴት እቀራለሁ
አንድ ቀን አንድ ቀን
ካልሽኝ ነገር ተርፎ
መሳፈሪያ ሳገኝ እኔም እመጣለሁ፡፡”
ግጥሙ የስደተኞችን እውነተኛ ስሜትና ብሶ ብቻ ሳይሆን ከአገር ከወጡ በኋላ ለመመለስ ምን ያህል እንደሚቸገሩ ይገልጻል፡፡ ስደተኛው ሀገር ውስጥ ያሉ ቤተሰቦቹንና ዘመዶቹን ቀዳዳ  ሊደፍን ሲፍጨረጨር እንዴት ለ‘ራሱ መሆን አቅቶት እንደሚቀር የሚያሳይ ነው፡፡ ገጣሚው ይህንኑ እውነት በሚያጎላ መልኩ “መሳፈሪያ ሳገኝ እኔም እመጣለሁ” በማለት ይደመድማል፡፡ ከቀዳዳው ብዛት የመሳፈሪያ እንኳን ለማግኘት ምን ያህል እንደሚቸገሩ የሚያሳይ ነው፡፡
የአብዛኛው ተሰዳጅ የስደት ምክንያት ኑሮን ማሸነፍ ነው፡፡ “የዕለት ጉርስ፣ የዓመት ልብስ” መቻልና እንጀራ ፍለጋ! …
ሀገር በቀል ስነ-ቃል እንዲህ ይላል፤
“እሄዳለሁ ብዬ ነገር አላበዛም
እንጀራ ነው እንጂ ሰው ሰውን አይገዛም፡፡
እንጀራ ሆነና የሰው ቁም ነገሩ
አልከበር አለ ሰው ሁሉ ባገሩ!”
ዓለም ፀሐይ ወዳጆ መታሰቢያነቱን ለስደተኞች ባደረገችው “የማታ እንጀራ” የግጥም መድበልዋ “ባርቀህ ትጮኸለህ” በሚል ርዕስ ስር፤ የስደትን ክትያዎችና በስደት ሲኖር የሚሰማውን ባይተዋርነት አስነብባናለች፡፡ ከዚሁ ግጥም ቀንጨብ አድርገን ተወሰኑ ስንኞችን በማንበብ እንሰናበት፡-
“ከእናትህ ማህፀን በጭንቀት ስትወጣ
አታውቀው ዓለም ውስጥ ሳትፈልግ ስትመጣ
እንደ ጮህከው ጩኸት ያኔ ስትወለድ
ዳግም ታለቅሳለህ ከሀገር ስትሰደድ
እንኳን የማያውቅህ የሚያውቅ ይረሳሃል
ለብሰህ ይበርድሃል ጠግበህ ይርብሃል
ብቸኝነት ማርኮ ኦና ያደርግሃል…”


Published in ህብረተሰብ
Saturday, 16 May 2015 10:46

የምርጫ ዋዜማ ወጋ ወጐች

“አሜሪካ - ሆሊዉድ
ህንድ - ቦሊውድ
ናይጄሪያ - ኖሊውድ
ኢትዮጵያ - ኑሮውድ!!”
እንግዲህ ወግም አይደለ…እስቲ 10 ዓመት ወደኋላ ተጉዘን ምርጫ 97 ላይ አረፍ እንበል፡፡ አይዟችሁ ምርጫውን ለመገምገም አይደለም፡፡ (ያኔ አልፏል!) ለመተቸትም እንዳይመስላችሁ፡፡ ለጨዋታ ነው፤ ለወጋ ወግ፡፡ እናላችሁ… ምርጫ 97 ከተጠናቀቀ ከጥቂት ወራት በኋላ (እስር፣ ስደት፣ ሞት፣ ወከባ መኖሩ ሳይረሳ ነው!) የቀድሞውን ጠ/ሚኒስትር (መሬት ይቅለላቸውና!) ጋዜጠኛ ይጠይቃቸዋል - ስለምርጫው፡፡
“ክቡር ጠ/ሚኒስትር፤ ምርጫው ትያትር ነበር ይባላል?”
በተረት፣ በሽሙጥ፣ በተረብ…ወዘተ የተኳሉ ምላሾች በመስጠት በእጅጉ የተካኑ የነበሩት የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ምን ቢሉ ጥሩ ነው?
“ትያትር አልነበረም፤ ደበበ እሸቱ በምርጫው ላይ በመሳተፉ ቲያትር የመሰላቸው ካሉ ተሳስተዋል”
እውነቱን ለመናገር ይሄ ነገር በትክክል እሳቸው ይናገሩት ወይም ሌላ ሰው በስማቸው ይፍጠረው የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ (ለዚህች እንኳን አያንሱም!)
ጠ/ሚኒስትሩ ለጉብኝት ወደ ቤልጂየም ሄደው ነበር አሉ፡፡ (ከምርጫ 97 በፊት ይሁን በኋላ አልታወቀም!) እዚያ በነበረው ስብሰባ ከተጋበዙት ኢትዮጵያውያን መካከል አንዷ (የአውሮፓ ሞልቃቃ ሳትሆን አትቀርም!) ሃሳብ ለመስጠት ተነሳች፡-
“የእርስዎ መንግስት አስጠሊታ ነው፤ ሥርዓታችሁ አስጠሊታ፤ አካሄዳችሁ አስጠሊታ፤ ባለስልጣኖቻችሁ አስጠሊታ፤ ሁለመናችሁ አስጠሊታ ነው” (ሃገሩ ቤልጂየም መሆኑ በጃት!)
ጠ/ሚኒስትሩም፤ “ጥሩ ነው! አስጠሊታ ልንሆን እንችላለን፡፡ አሁን እዚህ የመጣነው ግን ለቁንጅና ውድድር አይደለም፡፡” (የጨረሰች እኮ ናት!)
በ97 ምርጫ ሰሞን 22 ማዞሪያ ላይ ቁጭ ብለው የሚለምኑ አዛውንት የእኔ ብጤ (የእኔ ቢጤ” የምንለው Modest ለመሆን እኮ ነው!) ትዝ ይሉኛል፡፡ ምርጫው እየተሟሟቀ ሲመጣ ታዲያ እሳቸውም አንድ ሁለት የግል ጋዜጦችን እያነበቡ ነበር የሚለምኑት (የቅንጅት ደጋፊ ነበሩ ልበል!) እኔ የምላችሁ ግን… ሰዎች ባኮረፉ ቁጥር ስደትና መኮብለልን የሚመርጡት እንዴት ቢመራቸው ነው? (የመኢአድ አባላት ኤርትራ ገቡ ሲባል ሰምቼ እኮ ነው!) ቆይ ግን ያኮረፉ ተቃዋሚዎች ወደ ኤርትራ የሚጎርፉት ወዲ አፈወርቂ “የማኩረፊያ ካምፕ” አላቸው ማለት ነው? (የእሳቸው ወደኛ፤ የኛ ወደሳቸው ሆነ እኮ!)
እናላችሁ ግን… ዜጐች የኑሮ ውድነትና ድህነት አስመርሯቸው ሲሰደዱ…. ዝም!! ጭጭ!! ጋዜጠኞችና አሳታሚዎች የፈሩትን ፈርተው ሲሰደዱ…ዝም!! ጭጭ!! ተቃዋሚዎች በፖለቲካ ምህዳሩ ወይም በራሳቸው መጥበብ አሊያም በኢህአዴግ ካድሬዎች ዕብሪት ተማረው ሲሰደዱ ዝም!! ጭጭ!! እኔ የምፈራው ምን መሰላችሁ? እንዲህ እንደ አሸዋ የበተናቸውን ዜጎቻችንን በኋላ መሰብሰቡ ጭንቅ እንዳይሆንብን ነው፡፡ (ነው ወይስ አንፈልጋቸውም?)
የስደት ነገር ከተነሳ አይቀር አንዲት ሃሳብ ጣል አድርጌ ልለፍ፡፡ ዜጐች ከስደት ይልቅ አገር ውስጥ ሰርተው እንዲለወጡ መቀስቀስ፣ ማነቃቃት፣ ግንዛቤ መፍጠር… ሸጋ ነው፡፡ ግና ሁሉምን እየተነሳ ሹማምንት ያሉትን እንደበቀቀን መድገም ያሳፍራል። ያሳዝናል፡፡ ያስተዛዝባልም፡፡  (መፍትሄም አይሆንም!)
“ከሰው አገር ስደት እናት ጉያ ስር አሹቅ እየበሉ መኖር በስንት ጣዕሙ…” የሚሉት የጦቢያ ዝነኞች (Celebrities) ሲሆኑ ደግሞ ያናድዳል፡፡ (አሹቅንም… ስደትንም… ድህነትንም…. አያውቁትማ!)
አሁን ወደ ምርጫ ወጋ ወጋችን እንመለስ፡፡ እንዳልኳችሁ የምርጫ ዋዜማ ላይ ስለሆንን ገራ ገሩን ነው የምንጫወተው፡፡ ወጋ ወጉን!! (በህግ ዕውቀት ማነስ የሥነ ምግባር ጥሰት እንዳንፈጽም እኮ ነው!)
በነገራችን ላይ በ97 ምርጫና በዘንድሮው ምርጫ መካከል ያየሁት አንድ ጉልህ ልዩነት ምን መሰላችሁ? በ97 የፖለቲከኞች ስደት …. ኩብለላ …. እስር … ወዘተ የተከሰተው ከምርጫው በኋላ ነበር፡፡ በዘንድሮው ምርጫ ግን ከምርጫው በፊት ሆኗል፡፡ (ከተሳሳትኩ እታረማለሁ!)
ከምሬ እኮ ነው … አንዳንድ የመኢአድ አባላት “የሰላማዊ ትግል ጫማቸውን ሰቀሉ!” ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ (ጥሩ ምልክት ባይሆንም እንደ መረጃ ተቀብለነዋል!) እኔ የምላችሁ ግን ሰዎች እያኮረፉ ለስደት ሲዳረጉ (ፈልገውም ይሁን ተገደው!) የሚያግደረድር እንኳ ይጥፋ እንዴ! (እመኑኝ! 8ኛው ሺ ማለት አሁን ነው!)
አንዳንዴ ለምን እንደሆነ እንጃ … እዚህች አገር ላይ ሁሉ ነገር ድብልቅልቅ ይልብኛል፡፡ ለምሳሌ የሃይማኖት መሪዎችና የመንግስት ባለሥልጣናት፣ ቤተክህነትና የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር … ወጣትና የአገር ሽማግሌ … ድብልቅልቅ! (እኔ ብቻ ነኝ ልበል?!) ከመደበላለቅ ይጠብቃችሁ!! (የሃይማኖት መሪዎቹ ባለስልጣን ቅላፄ ሲናገሩ ምን ልበል?!)
ወደ ምርጫ ተመልሼአለሁ፡፡ ምን ሰማሁ መሰላችሁ… የእኛ አገር ፓርቲዎች አሁንም (እንደ 60ዎቹ) በአ“ቸ”ናፊ እና በአ“ሸ”ናፊ (በ“ቸ” እና “ሸ” እኮ ነው) መወዘጋገባቸውን አልተውም ይባላል? ሁለት ተቃዋሚ ፓርቲዎች የዘንድሮ የምርጫ ቅስቀሳ ሂደት ጅማሮ ላይ “የአዲሱ ትውልድ ፓርቲ” የምትለዋ አባባል ‹የእኔ ናት› በሚል መነታረካቸውን ሰምቼ ተስፋ ቆረጥኩ… በሆዴ! (ሌላው አብሮኝ ተስፋ እንዳይቆርጥ እኮ ነው!)
የቅስቀሳ ሳንሱር ደግሞ ትዝ አለኝ፡፡ (የ2007 ምርጫ ትውስታዬ ነው!) ቅሬታው የቀረበው ከኢዴፓ ነው፡፡ እናላችሁ … ኢዴፓ “መንግስት ሆኜ ከተመረጥኩ የፖለቲካ እስረኞችን በሙሉ እፈታለሁ” የሚል የቅስቀሳ መልዕክት ለEBC ይልካል፡፡ “የለም …. አይተላለፍም” ተባልኩ - ብሏል ኢዴፓ፡፡ (ከርቸሌ ውስጥ አመፅ ይቀሰቅሳል ተብሎ ይሆን?)
ሰሞኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት የምርጫ ሂደቱን የመገምገምያና የመቋጫ መድረክ በሒልተን ሆቴል አዘጋጅቶ ነበር፡፡ (ከስር ከስሩ መገምገም ዕዳ ያቃልላል!) እናላችሁ …. በግል ለመወዳደር አስበው በዕጣ የተጣሉት ወ/ሮ ሰሎሜ ታደሰ (የቀድሞ የኢቲቪ ሥራ አስኪያጅ!) በፕሮግራሙ ላይ የሰጡት የሰላ ሂስ አስደስቶኛል፡፡ (አንዳንዶች “Feminist” ናቸው ሊሉ ይችላሉ!)
እናላችሁ… ወ/ሮ ሰሎሜ የምርጫው ፍትሃዊነትና አሳታፊነት ላይ ነው ዱብዕዳ አስተያየት የሰነዘሩት። (የደነገጠ ግን የለም!) የምርጫ ቦርድ አባላት … በአዳራሹ ያሉት ተሳታፊዎች … ሚኒስትሩ …. ወዘተ ሁሉ ነገሩ በወንዶች የተሞላ መሆኑን ጠቁመው ሴቶችን የቱ ጋ ነው ያሳተፈው? ሲሉ ከአዳራሽ ሙሉ ወንድ ጋር ተገዳድረዋል፡፡ (የሰሎሜ ዓይነት ሃቀኛና ደፋር ያብዛልን!) የሚያሳዝነው ግን ወንዱ ሁሉ ቀልድ (Joke) እንደተነገረው ሰው ነው በሳቅ የፈረሰው፡፡ (አሳታፊነት ላይ ጥያቄ ማንሳት በየት አገር ነው የሚያስቀው?) በነገራችን ላይ እንደ ሰሎሜ ያሉ ጀግኖች ከምርጫ በዕጣ መገለላቸው ፌር አይደለም (ህግና ደንቡ ቢሆንም!)
ወደ ምርጫ ገራገር ልመልሳችሁ፡፡ ሰሞኑን በፌስ ቡክ ላይ ቀልቤን ከሳቡኝ ከምርጫ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች መካከል አንድ የኢህአዴግ ደጋፊ “ፌዝቡከር” ፖስት ያደረገው ምስል (ከንፈሯን ንቦች የከበቧት ሴት ናት!) ይገኝበታል፡፡ ከምስሉ ስርም፡-
“ማር ማር ይላል ከንፈርሽ
ለካስ ኢህአዴግ ነሽ” ይላል በግጥም፡፡
 የሰማያዊ ፓርቲ ደጋፊዎች ደግሞ “ግራም ነፈሰ ቀኝ ምርጫችን ሰማያዊ ነው” የሚል መፈክር ለጥፈዋል፡፡ (የፌስ ቡክ ጌታ ማርክ ዙከርበርግ ውሎ ይግባልን!!)
ከምርጫ ጋር ብዙም ግንኙነት የሌለው፣ ፈገግም ጨፍገግም የሚያደርግ ነገር ልንገራችሁና ልሰናበት (ምንጩ ፌስ ቡክ ነው!)
“አሜሪካ - ሆሊዉድ
ህንድ - ቦሊውድ
ናይጄሪያ - ኖሊውድ
ኢትዮጵያ - ኑሮውድ!!”
(አይገርምም… ጦቢያ በዓመት ይሄን ሁሉ ፊልም እያወጣች የፊልም መንደር የላትም!!)
በመጨረሻ በቴክስት ያለፍላጐታችን ከሚደርሱን መልዕክቶች ሰሞኑን የተላከልንን ለመሰናበቻ እነሆ፡፡
“Cheating in Examination is Killing a Generation!” ይላል (National Educational Assessment and Examination Agency) ከተባለ የመንግስት ተቋም የተላከው መልዕክት!)
እርግጥ ነው መኮረጅ ሃጢያት ነው (መንግሥት የሚኮርጀው ለፈተና ሳይን አገር ለመምራት ነው!) ግን እኮ Cheating   በፈተና ብቻ ሳይሆን በትዳርም (አመንዝራ ይባላል) በሥራ ቦታም፣ በጓደኝነትም፣ በምርጫም (ማጭበርበር ይባላል!) ወዘተ … ነውር ስለሆነ እናስወግደው!!
ስናሳርግ …. ምርጫው ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊና፣ ፍትሐዊ (ፍቅርም የሞላበት!) እንዲሆንልን አበክሬ እመኛለሁ፡፡ (በፀሎት የታገዘ ምኞት መሆኑን ልብ በሉ!)
ኢትዮጵያ ለዘላለም ታፍራና ተከብራ ትኖራለች። (ድንገት ብቅ ያለውን አርበኝነቴን ቻሉት!!)

“እዚህም ሞት እዚያም ሞት፤ ሁሉም ያው ነው”
“ኢትዮጵያውያን በአደገኛ ሁኔታ የሚደረገውን የስደት ጉዞ ይደፍራሉ” (ሂዩማን ራይትስ ዎች)
በየመን የባህር ዳርቻዎች በውሃ ተገፍተው የሚወጡ አስከሬኖችን የሚቀብር ድርጅት ተቋቁሟል፡፡ ከሟቾቹ ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት ኢትዮጵያውን ናቸው ከእጅ ወደ አፍ የሆነው የቤተሰቦቹ ኑሮ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ መሄዱ ተስፋ አስቆረጠው፡፡ ነገን ተስፋ በማድረግ ተምሬ ሰው እሆናለሁ በሚል ጥርሱን ነክሶ የገፋበት ትምህርቱ ለጥሩ ውጤት አብቅቶት ዩኒቨርሲቲ የመግባት ዕድል ቢገጥመውም ተመርቆ ድግሪውን ይዞ ሲወጣ ግን እንዳሰበው ሥራ ለማግኘት አልታደለም፡፡
አነስተኛ የቀን ሥራ በመስራት በሚያገኛት ጥቂት ገንዘብ ደካማ ቤተሰቦቹን ለመደጐም ብዙ ጥረት ደረገ፡፡ ሆኖም አልተሳካልኝም ይላል፡፡ እሱና ሁለት ታናናሽ እህቶቹ እንዲሁም የስኳር ህመምተኛ እናቱ ሰንጋተራ አካባቢ ከቀበሌ በ15 ብር ከ80 ሣንቲም በተከራዩት ባለሁለት ክፍል ደሳሳ ቤት ውስጥ ነበር የሚኖሩት፡፡ ይህቺ ደሣሣ ጐጆአቸው ግን በመልሶ ማልማት ሳቢያ እንደምትፈርስ ተነገረው፡፡ መርዶ ነበር የመሰለው፡፡ እናቱ ሲሰሙ ደግሞ በድንጋጤ የአልጋ ቁራኛ ሆኑ፡፡ በድህነት ላይ ረሃብ፣ በረሃብ ላይ በሽታ ተደራርበው አደካከሟቸው፡፡ አልጋ ላይ የዋሉትን፣ ህመምና ረሃብ የሚያሰቃያቸውን እናቱን የሚያደርገው አጣ፡፡ ሁሉም ነገር ከሚቋቋመው በላይ ሆነበት፡፡ ዕለት ተዕለት ተስፋ መቁረጡ እየተባባሰ መጣ፡፡ በዚህ መሃል ነው ከቀናት በፊት መርካቶ ጫማ ቤት አብረውት በቀን ስራ ከተቀጠሩ ጓደኞቹ የሰማው የስደት መንገድ ጆሮው ላይ ያንቃጨለው። “አሁን የእኔ መኖርና አለመኖር ለቤተሰቦቼ ምን ይጨምርላቸዋል? እንደውም ረዳት የላቸውም ተብሎ እንዳይታዘንላቸው እንቅፋት ነው የሆንኩባቸው፤ እናም መሄዴ ለእነሱም ጥሩ ነው” ሲል ለራሱ ደመደመ - ተስፋ የቆረጠው ወጣት፡፡ እናቱ እጅግ ለባሰ ቀን ብለው ያስቀመጧትን 8 ግራም የአንገት ሃብላቸውን ይዞ አብሮአደግ ከሆኑት የሰፈሩ ልጆች ጋር ለስደት ተነሣ፡፡ የስደቱን ነገር ለእናቱም ሆነ ለሁለት ታናናሽ እህቶቹ አልነገራቸውም፡፡በመተማ በኩል የሱዳን ድንበርን አቋርጠው ለመግባትና ወደ ሊቢያ ለመዝለቅ፣ ከዚያም የሜዲትራኒያን ባህርን በጀልባ አቋርጠው ጣሊያን ለመሻገር የሚችሉበት አቋራጭ መንገድ እንዳለ ነግሮ ባሳመናቸው ደላላ አማካኝነት ለጉዞ ተዘጋጁ፡፡ እዚሁ አዲስ አበባ አሜሪካን ግቢ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው የስደተኞች ማጠራቀሚያ ቤት ውስጥ ከአምስት ጓደኞቹ ጋር ገባ፡፡
ከአዲስ አበባ ተነስተው ወደ መተማ ጉዞ የጀመሩት ምሽት ላይ ነበር፡፡ ከአቅሟ በላይ ተሳፋሪዎችን የጫነችው ሚኒባስ፣ የምሽት ተጓዦቹን መተማ ለማድረስ በሰዓት 120 ኪሎ ሜትር ትፈተለክ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ጉዞው ነፍስ ውጭ ነፍስ ግቢ ቢሆንም እንደምንም መተማ ደረሱ፡፡ ወደ ሱዳን ድንበር የሚያደርሳቸውን፣ የሱዳንና የኢትዮጵያን ድንበር የሚያገናኘውን ገለባት የተባለ ድልድይ የሚያሻግራቸውን ደላላ ለሶስት ቀናትን ጠብቀው ካገኙት በኋላ ይዟቸው ሱዳን ገባ፡፡ እጅግ ዘግናኙን የሰሃራ በረሃ በእግር አቋርጠው ከበርካታ የስቃይና የመከራ ጉዞ በኋላ ሊቢያ ደረሱ፡፡ በዚህ ዘግናኝ ጉዞ መራራውን በረሃ መቋቋም አቅቷቸው፣ በረሃ የቀሩ በርካታ የጉዞ ጓደኞቹን ያስታውሳል፡፡ እንደ እሱ እድል ቀንቷቸው ሊቢያ መግባት የቻሉት ስደተኞች፤ የሜዲትራኒያንን ባህር በጀልባ አቋርጠው፣ ጣሊያን ለመግባት ሁለት መቶ ዶላር ከፍለው፣ አርጅታ ውልቅልቋ በወጣ ጀልባ ላይ ተሣፈሩ፡፡ ከአቅሟ በላይ የጫነችው የስደተኞች ጀልባ ጣሊያን ድንበር አካባቢ ለመድረስ ጥቂት ሲቀራት በቅኝት ላይ በነበሩ የጣሊያን ጀልባዎች እይታ ውስጥ ገባች፡፡ ይህንን የተረዱት የጀልባዋ ዘዋሪዎች ወደ ኋላ በመመለስ ጉዞ ወደመጡበት ሆነ። ከተያዙ የሚደርስባቸው ቅጣት የከፋ መሆኑን ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ወደተነሱበት የሊቢያ የወደብ ከተማ ተመልሰው የጫኑአቸውን ስደተኞች በማራገፍ ወደ የጉዳያቸው ሄዱ፡፡ ምስኪኖቹ ስደተኞች፤ ለጉዞው የከፈሉት ገንዘብ ግን የውሃ ሽታ
ሆኖ ቀረ፡፡ ከዚህ በኋላ ፍፁም ከሊቢያ ድንበር ለመውጣትና ወደ ጣሊያን ለመሻገር በተደጋጋሚ ያደረገው
ሙከራ ሳይሳካለት ቀረና ከፖሊስ እጅ ወደቀ፡፡ ከስድስት ወራት የእስር ቆይታ በኋላ በአለማቀፉ የስደተኞች ማህበር በኩል ወደ አገሩ እንዲመለስ ተደረገ፡፡ አዲስ አበባ ሲመለስ ግን ትቶት ወደሄደው ደሳሳ የእናቱ ጎጆ ለመመለስ ድፍረት አጣ፡፡ ነገ የተሻለ ደረጃ ላይ ደርሼ ህይወቷን እለውጣለሁ ብሎ ከእናቱ ጉያ የወሰደው የእናቱ የክፉ ቀን ቅርስ ተሸጦ ለህገወጥ ደላሎቹ ሲሳይ ሆኗል፡፡ ቤሳ ቤስቲን በኪሱ አልነበረውም። አዲስ አበባ ላይ ለጥቂት ቀናት ወዲያ ወዲህ ሲል ከቆየ በኋላ ግን አላስቻለውም፡፡ እሩህሩህ የእናት አንጀት ይቅርታውን እንደማይነፍገው አምኖ ይቅርታን ለመጠየቅ፣ አፈር ፈጭቶ ወዳደገበት መንደር ሲሄድ የጠበቀው የፍርስራሽ ክምር ነበር፡፡ ወጣቱ ከመሄዱ በፊት ቤቱ ለልማት እንደሚፈርስ ቢሰማም እንደ አዲስ በድንጋጤ ልቡ ለሁለት ክፍል አለ፡፡ ድንጋጤው በዚህ ብቻ ግን አላበቃም። የስኳር ህመምተኛ አሮጊት እናቱ ከወራት በፊት እስከወዲያኛው ማሸለባቸውንም ሰማ፡፡ የእናቱን መርዶ ችሎ ለመቀበል አቅም አጣ፡፡ የባህርና የበርሃ ሲሳይ ከመሆን ያመለጠባቸው አጋጣሚዎች እጅጉን ናፈቁት፡፡ “ምነው እዛው ሞቼ በቀረሁ፡፡” ሲል ክፉኛ ተመኘ፡፡ ጎጃም በረንዳ አካባቢ በሚገኘው የህገወጥ ሰዎች አዘዋዋሪ (ደላሎች) መናኸሪያ ውስጥ ያገኘሁት ይህ ወጣት፤ የስደት ህልሙን አስፈሪዎቹ የሰሀራ በረሃና የሜዲትራኒያን ስምጥ ባህር አላመከኑትም፡፡ ይልቁንም አገሩ ተመልሶ ያጋጠመውና ያየው ዘግናኝ ነገር ልቡን ይበልጥ አደንድኖት ዳግም ለስደት ንዲነሳሳ እንዳደረገው ይናገራል፡፡ ይኼ የ26 ዓመቱ ወጣት ሌት ተቀን ያገኘውን ሥራ በመሥራት ጥቂት ገንዘብ ቋጥሮ በሶማሊያ ቦሶሳ በኩል ወደ የመን ለመጓዝ መላ እያፈላለገ እንደሆነ ገልጿል፡፡ በቅርቡ በኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ የደረሰውን አሰቃቂ ሞትና መከራ አነሳሁበት፡፡ “እዚህም
ሞት እዚያም ሞት፤ ሁሉም ያው ነው” አለኝ ወጣቱ፤ ተስፋ በቆረጠ ስሜት ፍርጥም ብሎ፡፡   የኑሮ ውድነት፣ ሥራ አጥነት እና ተስፋ ቢስነት አስመርሯቸው፣ በደላሎች ጉትጐታ ተታለው ለስደት የሚነሱ ትዮጵያውያን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው፡፡ ከዓለማችን ታላላቅ በረሃዎች አንዱ የሆነውን የሠሃራ በረሃ አቋርጠው፣ በሊቢያ በኩል ወደ አውሮፓ የመግባት ተስፋን ያነገቡ፣ በፋርስ ባህረሰላጤ ወደ የመንና ጣሊያን ለመግባት የሞከሩ፣ በኬንያ በኩል ወደ ደቡብ አፍሪካ የመሄድ እቅድን የነደፉ በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በረሃው ውጦ አስቀርቷቸዋል፡፡ ባህሩም ውጧቸዋል። በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) የተደረገ አንድ ጥናት እንዳመለከተው፤ በ2004 ዓ.ም ወደ የመን ለመጓዝ በ228 ጀልባዎች ተሣፍረው ከነበሩ 14,486 ኢትዮጵያውያንና ሱማሊያዊያን ስደተኞች መካከል ስልሣ አምስቱ ሲሞቱ፣ ሠላሣ ስድስቱ የደረሱበት አልታወቀም፡፡ በአብዛኛው የስደት ጥንስሱ የሚጀመረው እዚሁ በመዲናችን አዲስ አበባ ውስጥ ነው፡፡ ከተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ሣውዲ አረቢያን፣ የመንን፣ ደቡብ አፍሪካንና ጣሊያንን መዳረሻ ህልማቸው አድርገው የሚነሱ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች፤ ለጉዞአቸው ዕቅድ የሚያወጡት አዲስ አበባ ውስጥ ከሚያገኟቸው ህገወጥ ደላሎች ጋር ነው። ይህ የአዲስ አበባው የድለላ መረብ እስከ ሱዳን፣ ሱማሊያና ሊቢያ ድረስ የዘለቀና በኔትወርክ የተሳሰረ ነው፡፡ ደላሎቹ ስደተኞቹን በጨው በረንዳ፣
ጐጃም በረንዳ፣ አሜሪካን ግቢ፣ ተክለሃይማኖት፣ ሰባተኛና ቦሌ ሚካኤል አካባቢ ላይ ለዚሁ ተግባር በተዘጋጁና ስደተኞችን ለማቆያ በሚያገለግሉ ቤቶች ውስጥ እያጠራቀሙ ለጉዞ ዝግጁ ያደርጓቸዋል፡፡ ስደተኞቹ ሁልጊዜም የስደት ጉዞውን የሚጀምሩት ምሽት ላይ ነው፡፡ ህልማቸው ወዳደረጉአቸው አገራት ከሚሄዱ የስደት ጓደኞቻቸው ጋር ዘግናኙን የመከራ ጉዞ ይጀምሩታል፡፡ በአብዛኛው የስደቱ ጉዞ በአራት ዋና ዋና መንገዶች የሚካሄድ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ በሊቢያ ጣሊያን፣ ከኢትዮጵያ ቦሳሶ ሱማሊያ የመን፣ ከሞያሌ ኬንያ ድንበር ደቡብ አፍሪካ እና አቦኮ፣ ኬላበር ጅቡቲ ዋንኞቹ የስደተኞች የጉዞ መዳረሻዎች ናቸው፡፡
ከአዲስ አበባ ተነስቶ መተማን አቋርጦ፣ በገለባት ድልድይ ሱዳን ድንበር በመግባትና የሰሀራ በረሃን በእግር አቋርጦ የባህር ላይ ጉዞ በማድረግ ጣሊያን ላይ በሚጠናቀቀው በዚህ የጉዞ መስመር ለመጓዝ ደላሎችን ፍለጋ የሚባዝኑ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄዱን በስደተኞች ድርጅት የተደረገው ጥናት ይፋ አድርጓል፡፡ በአብዛኛው ከደቡብ ወሎ፣ ከሚሴ፣ አላማጣ፣ ትግራይ፣ ጅማ፣ አርሲ፣ እንዲሁም ከደቡብ ክልል ሆሣህናና ሃዲያ አካባቢዎች የሚጓዙ ስደተኞች፤ የፑንት ላንዷን የወደብ ከተማ ቦሳሶ እንዳጨናነቋትና ሴቶቹ እጅግ አነስተኛ በሆነ ገንዘብ በወሲብ ንግድ ሥራ ላይ መሰማራታቸውን እንዲሁም ከUNHCR የሚሰጣቸውን የምግብ እርዳታ እየተቀበሉ ለአመታት ኑሮአቸውን እየገፉ እንደሆኑ አመልክቷል፡ከኢትዮጵያ በቦሳሶ ሶማሊያ፣ የመን በሚደርሰው በዚህ የስደት የጉዞ መስመር ተጉዘው ዕድል
የቀናቸው ጥቂቶች የመንን የመርገጥ ዕድል ሲያገኙ፣ ብዙዎች የባህር ሻርኮች ሲሳይ ሆነው ይቀራሉ።
ከአዳማ ተነስቶ የፑንትላንዷ የወደብ ከተማ ቦሳሶ ገብቶ፣ በኤደን ባህረሰላጤ በኩል ወደ የመን ለመግባት ሞክሮ ያልተሣካለትና ህይወቱ በተአምር እንደተረፈች የሚናገረው የ22 ዓመቱ ኢትዮጵያዊ ያሬድ በቀለ፤ ይህ የስደት መስመር እጅግ አደገኛ መሆኑን ይናገራል፡፡ ያሬድ በመንግስት አልባዋ ሱማሊያ በኩል ከአገር ለመውጣት በሚፈልጉ እጅግ በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ የሚፈፀመው ዘግናኝ ግፍ መሸከም ከሚቻለው በላይ መሆኑን ይገልፃል፡፡ አስገድዶ መድፈር፣ ዝርፊያና፣ ግድያ የተለመዱ ሲሆኑ በብዙዎቹ ስደተኞች ላይም በየዕለቱ የሚደርሱ ገጠመኞች እንደሆኑ ይናገራል። ከአዳማ በድሬደዋ፣ ሃረር፣ ጅግጅጋ፣ የቶጐ ጫሌን ኬላ አልፎ፣ ሱማሊያ ገብቶ ወደ ፑንትንላንዷ የወደብ ከተማ ቦሳሶ ደርሶ ወደ የመን የምታሻግረውን ጀልባ ጥበቃ ለአራት ወራት ያህል ቆይቷል፡፡ ለጀልባ መሳፈሪያው 120 ዶላር ከፍሎ በጀልባዋ ሲሻገርም ከተወለደበት አካባቢ ተነስተው እንደ እሱ የስደት ጉዞ ላይ ከነበሩ ሶስት ወጣቶች ጋር ተገናኝቶ ነበር፡፡ ጉዞአቸውን አጠናቀው አልወር ወደተባለችው የየመን ባህር ዳርቻ ለመድረስ ጥቂት ቀራቸው ጀልባዋ ተገለበጠች፡፡ በጀልባዋ ተጭነው ባህር ሲሻገሩ ከነበሩት ከ180 በላይ ስደተኞች ውስጥ በህይወት የተረፉት 27 ብቻ ነበሩ፡፡ በየመን ድንበር ጠባቂ ፖሊሶች ተይዞ ለጥቂት ቀናት በእስር ቤት ከቆየ በኋላ ወደመጣበት ሱማሌላንድ እንዲመለስ መደረጉን ይናገራል፡፡ በፑንትላንድ ቆይታውም እጅግ በርካታ
ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች እሱ ባለፈበት መንገድ እያለፉ፣ የመን ለመግባት ሙከራ ሲያደርጉ ባህሩ ውጦ እንዳስቀራቸው ይገልፃል፡፡ የዚህ አይነቱ እጅግ ዘግናኝ የስደት ጉዞ መስመር ዛሬም የበርካታ ኢትዮጵያውያን ሞት ምክንያት ቢሆንም አሁንም በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በየመውጫ በሩ ለስደት ይጣደፋሉ፡፡ ሂዩማን ራይትስ ዎች የተባለው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ሪፖርት እንደሚጠቁመው፤ ኢትዮጵያውያን በአደገኛ ሁኔታ የሚደረገውን የስደት ጉዞ ይደፍራሉ። ሴተኛ አዳሪነትና እጅግ አነስተኛ ሥራዎችን በመሥራት በድንበር አካባቢዎች ቆይተው ከአገር ለመውጣት ጥረት ያደርጋሉ፡፡
እንደ ሪፖርቱ፤ በባህር ተሻግረውና በረሃን አቋርጠው ለመግባት የሚሞክሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በየመን ባህር ዳርቻዎች የሚኖሩ ህዝቦች በውሃ ተገፍተው ወደ ባህሩ ዳርቻ የሚመጡትን አስከሬኖች የሚቀብር ድርጅት መስርተው በበጐ ፈቃደኝነት ይሠራሉ። ከሟቾቹ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙትም ኢትዮጵያውያን እንደሆኑ የሂዩማን ራይትስ ዎች ሪፖርት ይጠቁማል፡፡ እንዲህም ሆኖ ለስደት ያሰፈሰፉ በርካታ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ነው ያሉት፡፡ ወደ መከራ ጉዞ - ወደ ስቃይ ጉዞ - ወደ ሞት ጉዞ ተባብሶ ጨምሯል፡፡ መንግሥት፣ ተቃዋሚ  ፓርቲዎች፣ ሲቪል ማህበረሰቡ፣ ቤተሰብ፣ በአጠቃላይ ህዝቡ ይሄንን የዜጎችን ህይወት የሚቀጥፍ የስደት ጉዞ ለማስቆም በህብረት፣ ጥምረት ፈጥረው መትጋት ይኖርባቸዋል፡፡ ችግሩ መንግስት “በአገር ሰርቶ መክበር ይቻላል” ከሚለው በላይ እንደሆነ ሊታወቅ
ይገባል፡፡ በጥልቀትና በትኩረት መፈተሽና መመርመር ያለበት ትልቅ አገራዊ ችግር ነው፡፡ ትልቅ
አገራዊ ደዌ!! ትልቅ አገራዊ ቀውስ!!    

Published in ዜና

ገንዘብ ከፍለው መኪናቸውን ላልተረከቡ 115 ደንበኞች በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ አስረክባለሁ ብሏል፡፡

    ድርጅቱ በደረሰበት ከፍተኛ ኪሳራ ስራቸውን አቁመው ከአገር የተሰደዱት የ “ሆላንድ ካር” ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ታደሰ ተሰማ፤ መንግስት ባደረገላቸው ድጋፍና በተሰጣቸው የህግ ከለላ ከ3 ዓመት በኋላ ወደ አገራቸው መመለሳቸውን ገለፁ። ለመንግስት ያቀረቡት አዲስ ፕሮፖዛል ተቀባይነት ማግኘቱንና ወደ ሥራቸው በመመለስ መኪኖችን ሰርተው ለደንበኞቻቸው ለማስረከብ መዘጋጀታቸውን ገለፁ፡፡
ሥራ አስኪያጁ ከትናት በስቲያ በኢንተር ኮንትኔንታል ሆቴል ለጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ድርጅቱ ባጋጠመው ከ63 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሣራ አማካኝነት ሥራቸውን አቁመው ከአገር በመሰደድ ላለፉት 3 ዓመታት በተለያዩ የአውሮፓ አገራት የፋይናንስ ምንጭ ሲያፈላልጉ ቆይተዋል። በአሁኑ ወቅት ከተለያ ኩባንያዎች ባገኙት ገንዘብ ድጋፍና መንግስት ባደረገላቸው የህግ ከለላ ወደ አገራቸው መምጣታቸውን የተናገሩት ኢንጂነር ታደሰ፤ የኩባንያውን ሥራ ለማስቀጠልና ገንዘባቸውን ከፍለው መኪኖቻቸውን ላልተረከቡ 115 ደንበኞች በአጭር ጊዜ ውስጥ መኪኖቻቸውን ሠርቶ ለማስረከብ ዝግጅታቸውን አጠናቀው መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡
ቤልጂየም ብራሰልስ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አምባሳደር አቶ ተሾመ ቶጋ፤ ልዩ ድጋፍና ትብብር እንደተደረገላቸው የገለፁት ኢንጂነሩ፤ ኩባንያው የገጠመውን የፋይናንስ ችግር በመቅረፍ በተገቢው መንገድ ሥራቸውን እንደሚያከናውኑና በአጭር ጊዜ መኪኖችን አምርተው ለደንበኞቻቸው እንደሚያስረክቡ ገልፀዋል፡፡ ይህ ደግሞ “ሆላንድ ካር” እንዲያንሰራራና በሥሩ የሚተዳደሩ የነበሩት ከ250 በላይ ሰራተኞች የሥራ ዕድል እንደገና እንደሚከፍት ኢንጂነሩ ተናግረዋል፡፡   

Published in ዜና

ላለፉት አምስት አመታት በአፍሪካ ህብረት የኤርትራ ልኡክ ሆነው ያገለገሉትና ከአገሪቱ ከፍተኛ ዲፕሎማቶች አንዱ የሆኑት አምባሳደር ሞሃመድ ኢድሪስ ጃዊ፤ የኤርትራ መንግስት በዜጎቹ ላይ የሚፈጽመውን ጭቆናና የመብቶች ጥሰት በመቃወም በኢትዮጵያ ጥገኝነት መጠየቃቸውን ሮይተርስ ዘገበ፡፡
ፍትህና ነጻነትን ለመጎናጸፍ ለዘመናት የታገለው የኤርትራ ህዝብ፤ በኢ-ፍትሃዊ አገዛዝ ስር እየማቀቀ ይገኛል ያሉት አምባሳደሩ፤ ይህም የኤርትራን መንግስት የጭቆና አገዛዝ በመቃወም በኢትዮጵያ ጥገኝነት ለመጠየቅ ውሳኔ ላይ እንዳደረሳቸው ተናግረዋል፡፡
በኤርትራ የነጻነት ትግል ዘመናት በትግል ያሳለፉት አምባሳደር ሞሃመድ፤ኤርትራ ነጻነቷን ከተጎናጸፈች  በኋላም በተለያዩ ከፍተኛ የስልጣን ቦታዎችና በአህጉራዊ የዲፕሎማቲክ ስራዎች ላይ ለአመታት ማገልገላቸው ተነግሯል፡፡
የመብት ተሟጋች ቡድኖችና የተለያዩ ተቋማት፣ የኤርትራ መንግስት በመብቶች ጥሰትና በአስገዳጅ የወታደራዊ አገልግሎት ዜጎቹን እያሰቃየ ነው ሲሉ አገዛዙን ቢተቹም፣ የኤርትራ መንግስት ግን የሚሰነዘሩበትን መሰል የመብቶች ጥሰት ውንጀላዎች በተደጋጋሚ እንደሚያጣጥል አስታውሷል፡፡
የኤርትራ መንግስት ባለስልጣናት በአምባሳደሩ የጥገኝነት ጥያቄ ዙሪያ ያላቸውን አስተያየት እንዲሰጡት ያደረገው ሙከራ እንዳልተሳካለት ሮይተርስ ገልጧል፡፡

Published in ዜና

የብሪጅስቶን ጎማ አምራች ኩባንያ ምርቱን ተረክበው ለሚያከፋፍሉና ለሚቸረችሩ ደንበኞቹ በመሰረታዊ ጎማ አመራረትና አጠቃቀም እንዲሁም በጎማው መለያ ባህርያት ላይ የግማሽ ቀን ስልጠና ሰጥቷል፡፡
የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩን ያዘጋጀው በኢትዮጵያ የብሪጅስቶን ጎማ ወኪል የሆነው ካቤ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሲሆን በመድረኩ ላይ የብሪጅስቶን ጎማ አምራች ኩባንያ የመካከለኛው ምስራቅና አፍሪካ ተጠሪዎችና ስራ አስኪያጆች እንዲሁም የተለያዩ ሃገራት የኩባንያው ወኪሎች ተገኝተዋል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ በሸራተን አዲስ በተካሄደው በዚህ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ላይ የኩባንያው አዲስ ምርት የሆነው “ኢኮፒያ” የተሰኘ መለያ የተሰጠው የጎማ ምርትም ተዋውቋል፡፡
መድረኩን ማዘጋጀት ያስፈለገው ብሪጅስቶን ጎማ ነጋዴዎች ስለጎማቸው መሰረታዊ እውቀት እንዲያገኙ መሆኑን የጠቆሙት በካቤ ኃ/የተ/የግ/ኩባንያ የብሪጅስቶን ጎማ የቴክኒክ ክፍል ስራ አስኪያጅ አቶ ካሊድ አህመድ፤ ኩባንያው እንዲህ ያሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን ማዘጋጀቱ ደንበኞች ስለምርቶቹ ይበልጥ እውቀት እንዲያገኙና ምርጫቸው በእውቀት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ያደርገዋል ብለዋል፡፡
ብሪጅስቶን ጎማ ላለፉት 15 ዓመታት በኢትዮጵያ ገበያ የቆየ ሲሆን ከጊዜ ወደ ጊዜም የደንበኞቹ ቁጥር እየተበራከተና የገበያ ድርሻውን እያሰፋ እንደሚገኝ፣ በአለማቀፍ ደረጃም ተመራጭ ጎማ መሆኑን አቶ ካሊድ ተናግረዋል፡፡

Published in ዜና

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በርዝመቱ ከምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የሆነውን ህንፃ በአዲስ አበባ ለማስገንባት ከቻይናው የኮንስትራክሽን ኩባንያ ጋር ስምምነት መፈራረሙን ባንኩ አስታወቀ፡፡
ሕንፃው በጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታልና በኢትዮጵያ ሆቴል መካከል ባለው ስፍራ የሚሰራ ሲሆን 198 ሜትር ርዝመትና 43 ወለሎች እንዲሁም 1,500 መኪኖች ማቆም የሚችል 4 ቤዝመንት ወለል እንደሚኖሩት የባንኩ የኮሙኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤፍሬም መኩሪያ ገልፀዋል፡፡
ከዋናው ሕንፃ ጎን ሁለት ባለ 5 ፎቅ ሕንፃዎች እንደሚገነቡ የጠቀሱት አቶ ኤፍሬም፤ አንዱ የኮሜርሻል ሴንተር፣ ሁለተኛው የስብሰባ ማዕከል ነው ብለዋል፡፡ ትልቁ የስብሰባ አዳራሽ 2000 ሰዎች የመያዝ አቅም ሲኖረው፣ ሌሎቹ አዳራሾች 300 ሰዎች 5 አዳራሾች ደግሞ 200 ሰዎች እንደሚይዙና የዘመኑ የቴክኖሎጂ ውጤት የሆኑ መሳሪያዎች እንደሚገጠሙላቸው ጠቁመው ግንባታው ከሜይ 2015 ጀምሮ በ4 ዓመት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ አቶ ኤፍሬም ተናግረዋል፡፡

Published in ዜና

የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ በምግብ፣ በመጠጥና በእንስሳት መኖ በኢትዮጵያ አስገዳጅ ደረጃ በወጣላቸው ምርቶች ብቻ የደረጃዎች ምልክት እንዲሰጥ ለብሌስ አግሪ ፉድ ላቦራቶሪ ፈቃድ ሰጠ፡፡
ኤጀንሲው ለብሌስ አግሪ ፉድ ላቦራቶሪ በጻፈው ደብዳቤ፤ ከግንቦት 3 ቀን 2007 ጀምሮ በምግብ፣ በመጠጥና የእንስሳት መኖ በመሳሰሉ ምርቶች ላይ ኤጀንሲው ባዘጋጀው የሰርቲፊኬሽን መመሪያ መሰረት፤ በኢትዮጵያ ደረጃ በወጣላቸው ምርቶች ብቻ የደረጃዎች ምልክት እንዲሰጥ ፈቅዷል፡፡
ብሌስ አግሪ ፉድ ላቦራቶሪ በምግብ፣ በመጠጥና በእንስሳት መኖ በመሳሰሉ ምርቶች ላይ የላቦራቶሪ ፍተሻ፣ ኢንስፔክሽንና ሰርቲፊኬሽን አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን ላቦራቶሪው ዓለም አቀፍ እውቅና ያለውና ለአምራቾች፣ ለላኪዎችና ለአገልግሎት ሰጪዎች ተዓማኒነት ያለው አገልግሎት እንደሚሰጥ ታውቋል፡፡
ብሌስ ላቦራቶሪ በትምህርት ሚ/ር ቅድመ እውቅና ያለው ሲሆን በራሱ የሥልጠና ኢንስቲትዩት በሥነ - ምግብ፣ በምግብ ደህንነት፣ በተለያዩ ምግቦች አዘገጃጀትና የላቦራቶሪ አናሊስስ ስልጠና ይሰጣል፡፡   

Published in ዜና

የ16 አመቷን ታዳጊ ሃና ላላንጐን አስገድደው በመድፈር ለሞት አብቅተዋታል የተባሉት 5 ግለሰቦችን ፍ/ቤት ትናንት ጥፋተኛ ብሏቸዋል፡፡
የ10ኛ ክፍል ተማሪ የነበረችውን ታዳጊ ለ5 ቀናት አግተው በመያዝ እየተፈራረቁ መድፈራቸውን ፍ/ቤቱ በማስረጃ አረጋግጦ ጥፋተኛ ያላቸው 1ኛ የታክሲ ሹፌር:- ሳምሶን ስለሺ፣ በዛብህ ገ/ማርያም፣ በቃሉ ገብረ መድህንና የታክሲ ረዳቶቹ ኤፍሬም አየለና ተመስገን ፀጋዬ ናቸው፡፡
ተከሳሾቹ፤ ዕድሜያቸው ከ18 አመት በታች የሆነ ታዳጊን በመድፈርና በከባድ የሰው መግደል ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸው የነበረ ሲሆን የግራ ቀኙን ክርክር በዝግ ችሎት ሲመለከት የቆየው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት 3ኛ የወንጀል ችሎት በሁሉም ተከሳሾች ላይ የጥፋተኝነት ብይን ሰጥቷል፡፡
የመጨረሻ የቅጣት ውሣኔ ለመስጠትም ፍ/ቤቱ ጉዳዩን ለግንቦት 14 ቀጥሯል፡፡  

Published in ዜና
Page 10 of 19