Monday, 25 May 2015 08:48

በጨለማ ጥቅሻ

“ዲሞክራሲ ማለት ምርጫው ሳይሆን ቆጠራው ነው”

   ከዜጎች በቀር የሉአላዊ ስልጣን ባለቤት የሆነ ሌላ ምንም አይነት አካል የለም፡፡ መንግስታት ከዜጎች ይሁንታ ውጪ በሌላ በማንም አካል አይሾሙም አይሻሩምም። ይህ መሰረታዊ ከሆኑት የዲሞክራሲ ምሰሶዎች ውስጥ ዋነኛው ነው፡፡
የዜጎች ነፃነትና መብት እንዲጠበቅ፣ ብቸኛ የሉአላዊ ስልጣን ባለቤትነታቸው በማንም የማይደፈርና፣ የማይገሰስ መሆኑ በሁሉም አካላት ዘንድ ታምኖ፣ ተከብሮና ተረጋግጦ እንዲኖር ጠንካራና ነፃ የዲሞክራሲ ተቋማትን መገንባት ሌላ አማራጭም ሆነ አቋራጭ መንገድ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ከዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደቶች ውስጥ ቁልፉና ወሳኙ እንቅስቃሴ ነው፡፡
ካለፉት ስልሳ ዓመታት ጀምሮ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ነፃነታቸው፣ መብታቸውና የሉአላዊ ስልጣን ብቸኛ ባለቤትነታቸው የሚከበርበትና የሚረጋገጥበትን የዲሞክራሲ ስርዓት ለመገንባት መጠነ ሰፊ የህይወትና የአካል መስዋዕትነትን የጠየቀ እጅግ መራራ ትግል አካሂደዋል፡፡
ከ1990ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ በአፍሪካ መንፈስ የጀመረውን ሁለተኛውን የነፃነት ነፋስ ተከትሎ ሀገራችንን ኢትዮጵያን ጨምሮ ሰላሳ ሶስት የአፍሪካ ሀገራት አዲስ ባረቀቁት ህገ መንግስት ውስጥ ይህ ቁልፍ የዲሞክራሲ መሰረት እውቅናና ጥበቃ እንዲያገኝ ማድረግ ችለዋል፡፡
ይህ መልካም ክንዋኔ ነው፡፡ ይሁን እንጂ እንደ ወሳኝ እርምጃ ተደርጎ ሊቆጠር አይችልም፡፡ ለምን ቢባል? ህገመንግስታዊ እውቅና በማግኘቱ ብቻ የዜጎች መብት፣ ነፃነትና የሉአላዊ ስልጣን ብቸኛ ባለቤትነታቸው በተግባርም ይረጋገጣል ብሎ እርግጠኛ መሆን ስለማይቻል ነው፡፡ ማንኛችንም ብንሆን በቀላሉ መገንዘብ እንደምንችለው፣ ህገመንግስት መቅረጽና በተግባር መተርጎም ባህሪያቸውም ሆነ ነገረ ስራቸው ለየቅል ነው፡፡ በአንድ ህገ መንግስት ውስጥ እውቅና የተሰጣቸው የዜጎች መብትና ነፃነት በተግባር መከበርና መረጋገጥ የሚችሉት ህግ አውጭው፣ ህግ ተርጓሚውና ህግ አስፈፃሚው አካላት በህግ ተለይቶና ተገድቦ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት ሲችሉ ብቻ ነው፡፡
ቶም ስቶፓርድ የተባለው ትውልደ ቼክ እንግሊዛዊ ደራሲና ፀሐፌ ተውኔት ይህንን መሰረታዊ ጉዳይ በበለጠ ለማስረዳት፤ “ጀምፐርስ” በሚል ርዕስ በ1972 ዓ.ም ለእይታ ባቀረበው ተውኔት ውስጥ “ዲሞክራሲ ማለት ምርጫው ሳይሆን ድምጽ ቆጠራው ነው” የሚል መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ ይህን የመሰለውን የቶም ስቶፓርድን መልዕክት ሀሰት ነው ብሎ ማስተባበልም ሆነ ማናናቅ አይቻልም፡፡ የዜጎችን ድምጽ በህግ በተደነገገው መሰረት በአግባቡ ሳይቆጥሩ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ አካሂጃለሁ ብሎ መሸለል አይቻልም፡፡
እንግዲህ ዲሞክራሲ ማለት ምርጫው ሳይሆን ቆጠራው ነው ማለት በሌላ አነጋገር የዜጎችን ድምጽ ማክበር ወይም የዜጎችን ብቸኛ የሉአላዊ ስልጣን ባለቤትነት መቀበልና ማክበር ማለት ነው፡፡ ቀደም ብዬ ለመግለጽ እንደሞከርኩት፤ ይህን ወሳኝ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት እውን ለማድረግ፣ ከጠንካራና ነፃ የዲሞክራሲ ተቋማት ሌላ ቁልፍ መሳሪያ የለም፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ ያለ ጠንካራና ነፃ የዲሞክራሲ ተቋማት፣ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት መሞከር በጨለማ ሴት ልጅን እንደመጥቀስ ያለ ፋይዳ ቢስ ድካም ነው፡፡ በማንኛውም ዓይነት መመዘኛ ቢሆን ጠንካራና ነፃ የዲሞክራሲ ተቋማትን ሳይገነቡ ስለ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት አፍን ሞልቶ መናገርም ሆነ የዜጎችን መብት፣ ነፃነትና እኩልነት የሚያስጠብቅ፣ የሉአላዊ ስልጣን ባለቤትነታቸውንም የሚያረጋግጥ የዲሞክራሲ ስርአት ገንብቻለሁ እያሉ ነጋ ጠባ መሸለልም አንዲት ጠብታ ውሀ እንኳ የማይቋጥር፣ ከንቱ ጩኸት ነው፡፡
“የእልፍ አዕላፍ ታጋዮችን ክቡር ህይወት፣ ደምና አጥንት ገብሬ፤ የዜጎችን መብት፣ ነፃነትና እኩልነት አስጠብቄ፣ የሉአላዊ ነፃነት ብቸኛ ባለቤትነታቸውንም አረጋግጬበታለሁ” ማለት ብቻውን ዋጋ የለውም፡፡ በአንድ በኩል እንዲህ እያልን እየማልን የምንገዘትበትን ህገመንግስት በአግባቡ ልናከብረውና ልናስከብረው ይገባል፡፡
መቼም ጠንካራ፣ ነፃና ገለልተኛ የሆነ የምርጫ አስፈፃሚ ተቋም ሳይመሰርቱ ነፃና ፍትሀዊ ምርጫ ማካሄድና የዜጎችን ድምጽ በህግና በአግባቡ በመቁጠር የሉአላዊ ስልጣን ብቸኛ ባለቤትነታቸውን ማረጋገጥ እንደማይቻል ማስረዳት የአንባቢን የግንዛቤ አቅም እንደማሳነስ ይቆጠራል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይም በየጊዜው ሳናሰልስ መስራት ይገባናል፡፡ በየ5 ዓመቱ ምርጫ በመጣ ቁጥር በምርጫ አስፈፃሚ ተቋሙ ነፃና ገለልተኛ መሆን ላይ የሚያረብበውን የተቃዋሚዎች ጥርጣሬ የሚያጠፋ፣ ሁሉም እኩል እምነቱን የሚጥልበት ተቋም መፍጠር ለነገ የሚባል አይደለም፡፡ ዘወትር “ዲሞክራሲ ሂደት ነው” የሚለውም ሰበብ ከሆነ ጊዜ በኋላ ሂደትነቱ ማብቃቱ እንደማይቀር ማወቅ ብልህነት ነው፡፡

ነዋሪዎች በነገው ምርጫ ማን ሊያሸንፍ እንደሚችል ግምታቸውን ሰጡ

  በነገው እለት ለሚከናወነው 5ኛው አገራዊ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲያደርጉት የቆዩት ክርክርና የምረጡኝ ቅስቀሳ በትናንትናው እለት የተጠናቀቀ ሲሆን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በምርጫው ማን ሊያሸንፍ እንደሚችል ግምታቸውን ሰጥተዋል።
በኢትዮ ቴሌኮም የኢንጂነሪንግ ባለሙያ የሆነው ወጣት ጐሣዬ፤ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ በቴሌቪዥን የተላለፉ የፓርቲዎችን ክርክር እንደተከታተለ ጠቁሞ የሁሉም ፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳዎች  ሳቢነት ስለሚጐድላቸው ትኩረት እንዳልሰጣቸው ተናግሯል፡፡
እንዲያም ሆኖ ግን በመጨረሻ ቀን በውጭ ጉዳይና በደህንነት ዙሪያ የተደረገው ክርክር የተሻለ እንደነበር ያስታወሰው ጐሣዬ፤ መድረክና ሠማያዊ ፓርቲ ያቀረቧቸው መከራከሪያዎች ጠንካራ እንደነበሩ ገልጿል፡፡
በአብዛኞቹ ክርክሮች ላይ ኢህአዴግና ሠማያዊ እንዲሁም ኢዴፓ የተሻሉ ሆነው እንዳገኛቸው የጠቆመው አስተያየት ሰጪው፤ ኢህአዴግ በክርክሩ ጉድለቶቹን ማመኑ የሠለጠነ አካሄድ እየተከተለ መሆኑን ያመላክታል ብሏል፡፡ ሠማያዊ ፓርቲም በሚዲያዎች እንደሚነገረው ሃገር አጥፊ እንዳልሆነ፣ ይልቁንም ለሀገር የሚያስቡ ጠንካራ ፖለቲከኞች የተሰባሰቡበት መሆኑን እንደተገነዘበ ጐሳዬ ገልጿል፡፡
እንዲያም ሆኖ በምርጫው የሚያሸንፈው ኢህአዴግ መሆኑን አልጠራጠርም ይላል - ወጣቱ፡፡ ከተቃዋሚዎች በኩል በተለይ “ሠማያዊ” በርከት ያሉ ወንበሮችን የማሸነፍ እድል ሊኖረው እንደሚችልም ግምቱን ሰጥቷል፡፡
የ12ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ህሊና ይበልጣል፤ መገናኛ ብዙሃን የመከታተል ልምድ ያላት በመሆኑ ባለፉት ሳምንታት ማታ ማታ የሚተላለፉ የቅስቀሳ መልዕክቶችንና ክርክሮችን በቲቪ ስትከታተል መቆየቷን ትገልፃለች፡፡  “ሠማያዊ” ፓርቲ ያቀረባቸው መከራከሪያዎችም ቀልቧን እንደገዙት ትናገራለች። “እድሜዬ ስለማይፈቅድ የምርጫ ካርድ አልወሰድኩም” የምትለው ተማሪዋ፤ ሠማያዊ ፓርቲ ቢመረጥ ደስ እንደሚላት ገልፃለች፡፡ ለምን ስትባል? “ወጣቶች ስለሆኑ ደስ ይላሉ፤ የሚያቀርቡት ሃሳብም ማራኪ ነው” ብላለች፡፡
ሌላው የ12ኛ ክፍል ተማሪ በበኩሉ፤ ኢህአዴግ በቅስቀሳ መልዕክቶቹ ያቀረባቸው ጉዳዮች መልካም እንደሆኑ ጠቅሶ አሁንም ኢህአዴግ ሊመረጥ እንደሚችል ግምቱን ሰንዝሯል፡፡ “አዲስ ፓርቲ ስልጣን ቢይዝ ደስ ይለኛል” ያለው ተማሪው፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫ ወቅት ብቻ ስለሚንቀሳቀሱ በህዝቡ ውስጥ ዘልቀው ገብተዋል የሚል ግምት እንደሌለው ይናገራል፡፡
በዩኒቨርሲቲያቸው በተዘጋጀው የምርጫ ጣቢያ ድምፁን ለመስጠት የነገውን እለት እየተጠባበቀ መሆኑን የጠቆመው የአዲስ አበባ ሣይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ፣ የኤሌክትሪካል ኢንጅነሪንግ የ2ኛ አመት ተማሪው መስፍን አዱኛ፤ በምርጫ ቅስቅሳውም ሆነ በክርክሩ ኢህአዴግ ከተቃዋሚዎች የተሻለ ነበር ይላል፡፡ “ኢህአዴግ እንደሚያሸንፍም አልጠራጠርም” ብሏል፤ አስተያየት ሰጪው፡፡ እንዲያም ሆኖ ከተቃዋሚዎች ኢዴፓና ሠማያዊ ፓርቲ በክርክሮቹ ወቅት የተሻለ የመከራከሪያ ሃሳብ ሲያቀርቡ ነበር ያለው አስተያየት ሠጪው፤ ሌሎቹ ፓርቲዎች ከመከራከሪያ ርዕሶች የወጡ ሃሳቦችን በማንሳት ጊዜያቸው ሲያቃጥሉ ነበር ሲል ተችቷል፡፡
ኢዴፓና ሠማያዊ ከኢህአዴግ ቀጥሎ ምናልባት የፓርላማ ወንበር ሊያገኙ ይችላሉ ሲልም ግምቱን ሰጥቷል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ት/ቤት የ3ኛ ዓመት ተማሪ የሆነው ኪያ በበኩሉ፤ በተለይ በኦሮሚኛ ቋንቋ በቀረቡ የሚዲያ ክርክሮች “መድረክ” የበላይነት መያዙን ገልጿል። በኦሮሚያ ሬዲዮ በመሬት ፖሊሲ ላይ የቀረበው ክርክር መሣጭ እንደነበር ያስታወሰው ተማሪው፤ ተቃዋሚዎች ያቀረቡት መከራከሪያ ጠንካራ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ “መሬት አይሸጥም አይለወጥም ቢባልም በርካታ ገበሬዎች መሬታቸው በመንግስት ተነጥቆ ለባለሃብት እየተሸጠ ለችግር ተዳርገዋል” በሚለው የመድረክና ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች መከራከሪያ ላይ የኢህአዴግ ተወካዮች አጥጋቢ ምላሽ መስጠት እንዳልቻሉም ገልጿል፡፡  
ከምርጫ ቅስቀሳና ክርክሩ ውጭ መንግስትና የመንግስት መገናኛ ብዙሃን “ሠማያዊ”ን ለመወንጀል መሞከራቸው ተገቢ አይደለም ሲል የተቸው ተማሪው፤ “እኔ ስለሠማያዊ ፓርቲ ይበልጥ ለማወቅ የጓጓሁትና የነሱን የቅስቀሳ መልዕክቶች ለመከታተል ፍላጐት ያደረብኝ መንግስት ሠፊ ዘመቻ ከከፈተባቸው በኋላ ነው” ብሏል፡፡
መልዕክታቸውን ሲዳምጥም ሠማያዊ ፓርቲ እንደተባለው ሃገር አፍራሽ ሣይሆን አማራጭ ያለው ፓርቲ መሆኑን ተረድቻለሁ ይላል - ኪያ። “በየክርክር መድረኩ የቀረቡት የሠማያዊ ፓርቲ ተወካዮች ጠንካራ ተከራካሪዎች ነበሩ፤ በዚያ ላይ ወጣቶች መሆናቸው ቀልብ ይገዛል”፡፡ በማለት ወጣቱ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
በምርጫው ኢህአዴግ እንደሚያሸንፍ አጠራጣሪ ባይሆንም “መድረክ” እና “ሠማያዊ” በፓርላማው የተሻለ ወንበር ያገኛሉ የሚል ግምት እንዳለውም የጋዜጠኝነት ተማሪው ገልጿል፡፡
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ክፍል መምህር በበኩላቸው፤ በዘንድሮው ምርጫ ተቃዋሚዎች ከ97 ምርጫ ተዳክመው ቢቀርቡም ከ2002 የምርጫ ግን ተሽለው ቀርበዋል ብለዋል፡፡ በምርጫው ሂደት ላይ ከመገናኛ ብዙኃን አዘጋገብ ጋር የተያያዘ የዳሰሳ ጥናት እየሠሩ መሆኑን የጠቆሙት መምህሩ፤ መገናኛ ብዙሃን በተለይ ኢቢሲ ምርጫ ክርክሮችን በቀጥታ ስርጭት አለማስተላለፉና ታዳሚዎች በየክርክር መድረኩ ተገኝተው ጥያቄ እንዲያቀርቡ እድል አለመፍጠሩ ከሚጠበቅበት ሀገራዊ ተግባር አንፃር ውጤታማ ስራ እንዳልሠራ ይናገራሉ። በሌላ በኩል ተቃዋሚዎች የተሠጣቸው 9 እና 4 ደቂቃ ኢህአዴግን ከመተቸት ባለፈ የፖሊሲ አማራጫቸውን ለማቅረብ አላስቻላቸውም ብለዋል።
“ከዚህ አንፃር ሲገመገም ኢህአዴግ የተሠጠውን ሠፊ የአየር ሠአትና የቅስቀሳ ጊዜ ህዝብን በሚያሣምን መልኩ አልተጠቀመበትም” ያሉት መምህሩ፤ “ተቃዋሚዎች በተለይ ሠማያዊና ኢዴፓ የተሰጣቸውን የደቂቃዎች ሽርፍራፊ የህዝብን ቀልብ በሚገዛ መልኩ ተጠቅመውበታል” ብለዋል፡፡
ገዥው ፓርቲ እንደ መንግስትነቱ በየመገናኛ ብዙኃኑ የሚነገሩለት የልማት ዘገባዎች ለምርጫው በሠፊው ያግዙታል የሚሉት መምህሩ፤ ተቃዋሚዎች ግን ገና ሊሠሩ ያሰቡትን የሚያቀርቡ እንደመሆናቸው፣ ፖሊሲያቸውን በዝርዝር እንኳ ባይሆን በሚጨበጥ ደረጃ ማቅረብ የሚችሉበት የአየር ሰዓት ሊመደብላቸው ይገባ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡
“እነዚህን ሁሉ ከግምት ውስጥ ስናስገባ የገዥው ፓርቲ የክርክር ሃሳብ ከተቃዋሚዎች ይበልጥ ነበር ለማለት አያስደፍርም” ያሉት መምህሩ፤ በአጠቃላይ በቅስቀሳ በኩል ግን ኢህአዴግ የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረጉን አልካዱም፡፡
ኢህአዴግ በምርጫው በአብላጫ ድምጽ ሊያሸንፍ እንደሚችል የገመቱት መምህሩ፤ ተቃዋሚዎች በተለይ “ሠማያዊ” ፓርቲ በአዲስ አበባና በአማራ ክልል እንዲሁም “መድረክ” በኦሮሚያና በደቡብ በርከት ያሉ ወንበሮችን የማሸነፍ ዕድል አላቸው ብለው እንደሚያምኑ  ግምታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በንግድ ሥራ የሚተዳደሩት አቶ ይልማ፤ “ሠማያዊ” ፓርቲ ያቀረባቸው መከራከሪያዎችና የቅስቀሳ መልዕክቶች ከየትኛውም ተቃዋሚ የተሻለ ሆኖ እንዳገኙት  ጠቁመው ፓርቲው በዘንድሮ ምርጫ ባይሣካለት እንኳ በቀጣይ ምርጫዎች ተስፋ የሚጣልበት ነው ብለዋል -የዘንድሮን ምርጫ ኢህአዴግ እንደሚያሸንፍ በመገመት፡፡
ከፓርቲ አባልነት ራሳቸውን ያገለሉት የቀድሞ የኢዴፓ ፕሬዚዳንት አቶ ሙሼ ሰሙ በበኩላቸው፤ ፓርቲዎች ያካሄዷቸውን ክርክሮችና የምረጡን ቅስቀሳዎች ከሞላ ጐደል መከታተላቸውን ጠቁመው በክርክሮቹ ግለሰቦች ፓርቲያቸውን ወክለው ቢቀርቡም ከግል ብቃት አንፃር የፓርቲውን ሙሉ ሃሳብ ላያንፀባርቁ ይችላሉ ብለዋል። “የተመደበውም የአየር ሰዓት እንኳንስ ሃሳብ ለማቅረብ በሁለት ገጽ የቀረበን ጽሑፍ እንኳ አንብቦ መጨረስ የማይቻልበት ነው” ሲሉም ተችተዋል፡፡
“አንድ ሰው በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ጉዳይ ላይ ለመናገር እንዴት ነው 6 ደቂቃ የሚበቃው?” ሲሉ የሚጠይቁት አቶ ሙሼ፤ በዚህ ምክንያት ብቻ ተቃዋሚዎችን ሠፊ የቅስቀሳ እድል ካለው ኢህአዴግ ጋር ለማነፃፀር አስቸጋሪ ነው ይላሉ፡፡
ፓርቲዎች በገንዘብ አቅም ከፍተኛ ልዩነት እንዳላቸው የጠቀሱት የቀድሞ የኢዴፓ ፕሬዚዳንት፤ ኢህአዴግ ለቅስቀሳዎቹ ትላልቅ በጀት የሚጠይቁ ዶክመንተሪዎችን ሲሠራ፣ ተቃዋሚዎች ባንፃሩ ይህን ማድረግ ሣይችሉ መቅረታቸውን እንደታዘቡ ይናገራሉ፡፡
በክርክሮች ላይ ለኢህአዴግ ሠፊ ሰአት፤ ለተቃዋሚዎች የማታፈናፍን ደቂቃ መሰጠቱን የተቃወሙት አቶ ሙሼ፤ “ምርጫ” ወደፊት ፓርቲዎች ሊሠሩ ያሰቡትን እያቀረቡ ህዝብ እንዲፈርዳቸው የሚወዳደሩበት  ፈተና በመሆኑ ለሁሉም እኩል ሰአት መሠጠት ነበረበት ባይ ናቸው። ኢህአዴግ ላለፉት 5 አመታት የሠራውን ሲያወራ ከርሟል ያሉት አቶ ሙሼ፤ ፓርቲዎች ወደፊት እንሠራለን ብለው ለሚገቡት ቃል ኪዳን ግን ሁሉም እኩል ሰአት ሊሰጣቸው ይገባል ይላሉ፡፡
በቴሌቪዥን በቀረቡት ክርክሮች፤ የጣቢያው ሠራተኞች ብቻ ጠያቂና አወያይ ሆነው መቅረባቸው ተገቢ አይደለም ያሉት የቀድሞው ፖለቲከኛ፤  ከየሙያ ዘርፉ ጠንካራ ሰዎች ተመርጠው ሞጋች ጥያቄዎችን ለፓርቲዎቹ እያቀረቡ ክርክሩ መካሄድ እንደነበረበት ይጠቁማሉ፡፡ ለምርጫ ቅስቀሳ ፓርቲዎች ተመጣጣኝ የፋይናንስ አቅም ሊኖራቸው እንደሚገባም የተናገሩት አቶ ሙሼ፤ መንግስት በዚህ ረገድ ብዙ መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል። ኢህአዴግ ከጊዜ ወደ ጊዜ አባላቱ እየጨመሩ ሲሄዱ አቅሙ በዚያው ልክ እየሠፋ የሚሄድ ከሆነና ተቃዋሚዎች ይህን ማድረግ የሚችሉበት መንገድ ከሌለ ሁሌም አቅም ያለው አሸናፊ እየሆነ እንደሚሄድም አብራርተዋል፡፡
በክርክር መድረኮቹ ከሚታየው የጊዜ እጥረት ባሻገር ተቃዋሚዎች የሚጠበቅባቸውን ያህል ተዘጋጅተው ቀርበዋል ለማለት አያስደፍርም የሚሉት አቶ ሙሼ፤ ኢህአዴግም ቢሆን ሁሌ ከሚናገረው የተለየ ሃሳብ ይዞ አልቀረበም ሲሉ ተችተዋል፡፡
በምርጫ ውድድሩ ኢህአዴግ በተወሰኑ ከተሞች ላይ ጠንከር ያለ ፉክክር እንደሚገጥመው ግምታቸውን ያስቀመጡት አቶ ሙሼ፤ በምርጫው ላይ ያልተገባ ተጽእኖ ካልተፈጠረ ተቃዋሚዎች በአዲስ አበባ፣ ሃዋሣና በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች ላይ ድምጽ የሚያገኙበት እድል ሊኖር ይችላል ብለዋል፡፡ በአጠቃላይ ግን ኢህአዴግ አሁንም ሊያሸንፍ እንደሚችል የገመቱት  አቶ ሙሼ፤ ተቃዋሚዎች በጥምረት ካልሠሩ በቀር መንግሥት ለመሆን አይችሉም ብለዋል፡፡
መንግስት ለመሆን ቢያንስ 273 እጩዎችን ማስመረጥ እንደሚያስፈልግ የጠቀሱት አቶ ሙሼ፤ ፓርቲዎች በጥምረት መስራትን አብዝተው ሊያስቡበት ይገባል ብለዋል፡፡ እስከዚያው ግን ሠፊ የወንበር ቁጥር ይዞ መንግስትን መሞገትና ማስጨነቅም እንደ አንድ ፖለቲካዊ ድል ይቆጠራል ያሉት አስተያየት ሰጪው፤ እስካሁን ያለው የምርጫ ዘመቻ ለኢህአዴግ በቂ ስለሆነ በድምጽ መስጫውና ከዚያ በኋላ ባሉት ቀናት ፓርቲው እጁን መሰብሰብ አለበት ሲሉ አሳስበዋል፡፡
በአንድ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ በከፍተኛ አማካሪነት የሚሠሩት ዶ/ር ሲሳይ በበኩላቸው፤ ክርክሮቹ በዝግ ስቱዲዮ በቀረፃ የተከናወኑ በመሆናቸው ትኩረት ሰጥተው ለመከታተል ፍላጐት እንዳልነበራቸው ጠቁመው ሁኔታው የሀገሪቱ የምርጫ ስርአት ገና ብዙ የሚቀረው ጉዳይ እንዳለ አመላካች መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአሸናፊነቱን ግምት ለኢህአዴግ እንደሚሠጡ የገለፁት አስተያየት ሰጪው፤ ኢህአዴግ እንዳለፈው ምርጫ በአውራነት የሚቀጥል ከሆነ የሀገሪቱ ዲሞክራሲና የመድብለ ፓርቲ ስርአት ይበልጥ አደጋ ውስጥ እንደሚወድቅ አመላካች ይሆናል ብለዋል፡፡ ተቃዋሚዎች ሠፋ ያለ ወንበር አግኝተው የተለያዩ ሃሳቦች የሚንሸራሸሩበት ፓርላማ ለማየትም ተስፋ እንደሚያደርጉ አስተያየት ሰጪው አክለው ተናግረዋል፡፡      

     የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኢትዮጵያ በእስር ላይ የሚገኙትን የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌን አያያዝና የወቅቱን አጠቃላይ ሁኔታቸውን በተመለከተ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ማስታወቁን ዘ ጋርዲያን ትናንት ዘገበ፡፡
የተመድ የግርፋትና ስቃይ መከላከል ልዩ ክፍል ባልደረባ የሆኑት ጁአን ሜንዴዝ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ በየመን አውሮፕላን ማረፊያ በቁጥጥር ስር ውለው ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ የተደረጉት አቶ አንዳርጋቸው፣በአሁኑ ወቅት ያሉበትን ሁኔታና አያያዛቸውን እየመረመሩ እንደሚገኙ ለእንግሊዝና ለኢትዮጵያ መንግስታት በጻፉት ደብዳቤ አሳውቀዋል ያለው ዘገባው፤ግለሰቡ እንቅልፍ እንዳያገኙ ተደርገዋል፣ ለብቻቸው ታስረዋል የሚሉ ክሶች እየቀረቡ እንደሚገኙም አስታውሷል፡፡
ተቀማጭነቱ በለንደን የሆነውና በመላ አለም የሞት ፍርድ የተጣለባቸውን እንግሊዛውያን ሁኔታ የሚያጠናው ሪፕራይቭ የተባለ ተቋም የአጣሪ ቡድን ዳይሬክተር ማያ ፎኣ በበኩላቸው፣ አቶ አንዳርጋቸው በህገወጥ በመንገድ መያዛቸውንና ለኢትዮጵያ ተላልፈው መሰጠታቸውን ጠቅሰው፣ ለአንድ አመት ያህል ባልታወቀ ቦታ ታስረው እንደሚገኙና ተመድም የአቶ አንዳርጋቸውን አያያዝ ለማጣራት መወሰኑ አግባብነት እንዳለው ተናግረዋል፡፡
የእንግሊዝ መንግስት ለጉዳዩ የበለጠ ትኩረት በመስጠት ጠንካራ እርምጃዎችን መውሰድ ይገባዋል ያሉት ዳይሬክተሯ፣ አቶ አንዳርጋቸው አለማቀፍ ህጎችን በሚጥስና አብዛኛዎቹን የፍትህ መርሆዎች ባላከበረ መልኩ በእስር ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰው ግለሰቡ በአፋጣኝ ከእስር እንዲፈቱ ግፊት እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
የአቶ አንዳርጋቸው ጠበቃ የሆኑት ቤን ኩፐር በበኩላቸው፤ግለሰቡ በህገወጥ መንገድ በሌሉበት በተላለፈባቸው የሞት ቅጣት ያለአግባብ መታሰራቸውንና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ጠቅሰው፣ የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ቢሮም የተመድን የምርመራ ጅምር በመከተል ከእስር የሚለቀቁበትን ሁኔታ መፍጠር ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡
በለንደን የሚኖሩት የአቶ አንዳርጋቸው ባለቤት የሚ ሃይለማርያም በበኩላቸው፤ ባለቤታቸው በቁጥጥር ስር ከዋሉበት ጊዜ አንስቶ አንድ ጊዜ ብቻ በስልክ እንዳነጋገሯቸውና የት ቦታ ታስረው እንደሚገኙ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ተናግረዋል፡፡
በእንግሊዝ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በበኩሉ፤ ግንቦት ሰባት በአገሪቱ ፓርላማ በአሸባሪነት የተመዘገበ ድርጅት መሆኑንና ዋና ጸሃፊው የነበሩት አቶ አንዳርጋቸውም በአገሪቱ ሽብርና ብጥብጥ እንዲፈጠር በማሴርና ሽብርተኞችን በኤርትራ ውስጥ በማሰልጠን፣ በፋይናንስ በማገዝና በማቀናጀት ስርአቱን ለመናድ በማቀድ ወንጀል ተከሰው ጥፋተኛ በመሆናቸው የሞት ፍርድ እንደተፈረደባቸው አስታውቋል፡፡ የእንግሊዙ ጠ/ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን በቅርቡ ለኢትዮጵያ አቻቸው ለጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በጻፉት ደብዳቤ፤ ግለሰቡ ከእስር እንዲፈቱ ቢጠይቁም አዎንታዊ ምላሽ አለማግኘታቸውን በቅርቡ መዘገባችን ይታወቃል፡፡

Published in ዜና

በነገው ዕለት የሚካሄደው 5ኛው አገር አቀፍ ምርጫ፣ በደቡብ ክልል ከፋ ዞን ቦንጋ ከተማ፣ ጊምቢ ምርጫ ክልል ላይ እንደማይደረግና ምርጫው ላልተወሰነ ጊዜ መተላለፉን ምርጫ ቦርድ አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ በቀና ከትናንት በስቲያ በሒልተን ሆቴል ጉዳዩን አስመልክቶ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፤ “በክልሉ ምርጫው በዕለቱ የማይካሄድ ሲሆን ላልተወሰነ ጊዜ እንዲተላለፍ ተደርጓል” ብለዋል፡፡ ምክንያቱን የተጠየቁት ፕሮፌሰር መርጋ፤ “ይህ በጣም ተራና ቁብ የማይሰጠው ጉዳይ ነው፤ ለጋዜጣዊ መግለጫም የሚበቃ አይደለም” ሲሉ መልሰዋል፡፡
ምርጫው እንዲተላለፍ የተወሰነበት የከፋ ዞን ቦንጋ ከተማ፣ ጊምቢ ምርጫ ክልል፤ የግል እጩ ተወዳዳሪው ዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስ፤ ከደህዴን ኢህአዴግ እጩ ተወዳዳሪ ዶ/ር መብራቱ ገ/ማርያም ጋር የሚፎካከሩበት እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ምንጮች እንደሚሉት፤ ለፉክክር የቀረቡት የሁለቱ ወገኖች ደጋፊዎች ግጭት መፍጠራቸውና ግጭቱ እየተባባሰ መሄድ ለምርጫው መተላለፍ ዋና ምክንያት ሆኗል፡፡
የቦርዱ ሰብሳቢ ፕ/ር መርጋ በቃና፤ “በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ችግሮችን ፈር አስይዘን ምርጫው ይካሄዳል” ብለዋል፡፡ ተፈጠረ ስለተባለው ግጭትም ሆነ ሌላ ምክንያት የቦርዱ ኃላፊ ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡  

Published in ዜና

በአንድ ሳምንት 20 የሚደርሱ ፕሮጀክቶች ሲመረቁ፤ ከ10 በላይ የመሰረት ድንጋይ ተጥሏል


ያለፉት ጥቂት ሳምንታት ለኢህአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣናት የውጥረት ጊዜ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ከመደበኛ ሥራቸው ውጭ ከምርጫ ጋር የተገናኙ እንቅስቃሴዎችንም ሲያከናውኑ ሰንብተዋል። የኢህአዴግ ሊቀመንበርና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለሆኑት አቶ ኃይለማርም ደሳለኝም ሁኔታው የተለየ አልነበረም፡፡ ያለፉትን ሳምንታት ለአዳዲስ ፕሮጀክቶች የመሰረት ድንጋይ በመጣልና የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን በመመረቅ ተወጥረው ነው ያሳለፉት። በአዲስ አበባና ክልል ከተሞች በአንድ ሳምንት ውስጥ 20 የሚደርሱ ፕሮጀክቶች የተመረቁ ሲሆን ከ10 በላይ ለሚሆኑ አዳዲስ ፕሮጀክቶች የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል፡፡
ባለፈው ሰኞ ማለዳ በአዳማ ከተማ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በ340 ሄክታር መሬት ላይ ለሚገነባው የኢንዱስትሪ ፓርክ የመሰረት ድንጋይ ያስቀመጡ ሲሆን የአዲስ አበባ ሚኤሶ የባቡር መንገድ ግንባታ የሃዲድ ዝርጋታ ፕሮጀክትንም መርቀዋል፡፡ የዚያኑ እለት ረፋዱ ላይ ደግሞ 102 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል ያመነጫል የተባለውን የአዳማ ቁጥር 2 የንፋስ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት እንደመረቁ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ፅ/ቤት ድረ ገፅ ይጠቁማል፡፡
በነጋታው ማክሰኞ ጠ/ሚኒስትሩ ወደ ጂማ በማምራት ለጅማ የኢንዱስትሪ መንደር ግንባታና ለጅማ ባቡር ጣቢያ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ አኑረዋል፡፡ በዚህ ብቻ አላበቁም፡፡ የጅማ ቦንጋ 110 ኪሎ ሜትር የአስፓልት ኮንክሪት መንገድን እንዲሁም ከ250 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተከናወነውን የጅማ አባጅፋር አውሮፕላን ጣቢያ የማስፋፊያ ፕሮጀክትም መርቀዋል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ የዚያኑ እለት ወደ ድሬደዋ ተሻግረውም በ1 ቢሊዮን ብር ይገነባል ለተባለው ዘመናዊ ስታዲየም እንዲሁም ለኢንዱስትሪ መንደር ግንባታ የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል፡፡
ከሳምንት በፊት ረቡዕና ሐሙስ ደግሞ አምቦ ነቀምት ነበሩ፡፡ በአምቦ የባቡር ጣቢያ የመሰረት ድንጋይ ያስቀመጡ ሲሆን በነቀምት የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ አኑረዋል፡፡ ከዚያው ከነቀምት ሳይወጡም የብረት ማዕድን አውጥቶ ብረት ለሚያመርት ፋብሪካ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል፡፡
ባለፉት ሳምንታት ሜጋ ፕሮጀክቶች ብቻ አልነበሩም የተመረቁት፡፡ ከት/ቤት አንስቶ እስከ የመጠጥ ንፁህ ውሃ ድረስ ተመርቋል፡፡ ባለፈው ማክሰኞ የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ያስገነባቸውን የአንደኛ ደረጃ ት/ቤት፣ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የገበያ ማዕከላት እንዲሁም የወጣቶች ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ያስመረቀ ሲሆን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በበኩሉ፤ በጀሞ 1 እና በቦሌ ሳይት ኮንዶሚኒየም ቤቶች አካባቢ ያስገነባቸውን ት/ቤቶች ረቡዕ እለት አስመርቋል፡፡
በደቡብ ክልል ሲዳማ ዞን በ149 ሚሊዮን ብር የተገነባው የአዋዳ - ቦርቻ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የተመረቀ ሰሆን የንፁህ ውሃ ፕሮጀክቱ በ43 ቀበሌዎች የሚኖሩ 257 ሺህ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል፡፡ በዚያው በደቡብ ክልል በስልጤ ዞን፣ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን እና የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈርጌሣ፤ የጠጠር መንገድ እና የሆስፒታል ግንባታ ፕሮጀክቶችን መርቀዋል፡፡   
በአዲስ አበባ በአዲስ ከተማ ክ/ከተማ ለሚገነባው ዘመናዊ ሆስፒታል የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠ ሲሆን አዲስ ለሚገነባው የብሔራዊ ቲያትር ህንፃም እንዲሁ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠው በእነዚሁ ሳምንታት ነው፡፡  
በሌላ በኩል ተቃዋሚዎች፤ በምርጫው ዋዜማ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ በርካታ ፕሮጀክቶች መመረቃቸውና የመሠረት ድንጋይ መጣሉ የኢህአዴግ የምርጫ ቅስቀሳ ስትራቴጂ አካል ነው ሲሉ ይተቻሉ፡፡ የኢህአዴግ ጽ/ቤት የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሃላፊ አቶ ደስታ ተስፋው በበኩላቸው፤ “የፕሮጀክቶቹ መመረቅም ሆነ ለአዳዲስ ፕሮጀክቶች የመሠረት ድንጋይ መጣሉ ፈጽሞ ከምርጫው ጋር የሚገናኝ አይደለም፣ የመንግስት የእለት ተእለት ተግባር አካል ናቸው” ብለዋል፡፡
መንግስት የሠራቸውን ፕሮጀክቶች ቀደም ብሎም በተከታታይ ሲያስመርቅ ነበር ያሉት ኃላፊው፤ ህዝቡ ኢህአዴግን የሚመርጠው በተመረቁት ፕሮጀክቶች ብቻ አይደለም፤ በተከታታይ ያከናወናቸውን ጠንካራ ስራዎች መዝኖ ነው ብለዋል፡፡ “ምርጫውን ማንም ቢያሸንፍ ልማት አይቆምም” ያሉት የኢህአዴግ ጽ/ቤት ሃላፊው፤ “የምርጫው ውጤት እስኪታወቅ ድረስ መንግስት እጁን አጣጥፎ እንዲቀመጥ መፈለግ ትክክል አይደለም፤ ለምርጫ ተብሎ የሚመረቅ ፕሮጀክት የለም፤ ምርጫ ነው ብለንም ልማት አናቆምም” ብለዋል፡፡
በርካታ ፕሮጀክቶች ከዚህ ቀደምም ተመርቀዋል፤ የመሠረት ድንጋይም ተጥሎላቸዋል ያሉት ኃላፊው፤ በአጋጣሚ በምርጫው ሰሞን የተመረቁትን ብቻ አጉልቶ ወደ ሌላ ትርጉም መውሰድ ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡

Published in ዜና

በዘንድሮው 5ኛ አገር አቀፍ ምርጫ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ በደቡብ ክልል በወላይታ ዞን በቦሎሶሶሬ ሁለት ምርጫ ክልል ከሰማያዊ ፓርቲ እና ከአዲስ ትውልድ ፓርቲ  እጩ ተወዳዳሪዎች ጋር ይፎካከራሉ፡፡ በክልሉ የመድረክ እጩ የነበሩት አቶ ተስፋ ኃይሌ ከምርጫው ራሳቸውን አግልለዋል፡፡ በ2002 ምርጫ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በተወዳደሩበት የአድዋ ከተማ ምርጫ ክልል ደግሞ ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ከመድረክ እጩ ጋር የሚወዳደሩ ሲሆን፤ የመድረኩ ዶ/ር መረራ ጉዲናም በኦሮሚያ ምዕራብ ሸዋ ቶኬ ኩታዬ አምቦ 2 ምርጫ ክልል ከኢህአዴግ ኦህዴድ እጩ ጋር እንደሚወዳደሩ ታውቋል፡፡ በዚሁ ክልል አርሲ ዞን ኢታያ ምርጫ ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ አባዱላ ገመዳ ከአንድነትና ከአትፓ እጩ ተወዳዳሪዎች ጋር ይፎካከራሉ፡፡ በአማራ ክልል ምዕራብ ጐጃም ዞን ጢስአባይ ምርጫ ክልል የኢዴፓው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ ለምርጫ ይወዳደራሉ፡፡ በዚሁ አማራ ክልል ጐንጂ ምርጫ ክልል፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ ወ/ሮ ሽታዬ ምናለ የሚወዳደሩ ሲሆን በአዊ ዞን ቻግኒ ምርጫ ክልል ደግሞ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከኢራፓና አንድነት እጩዎች ጋር ይፎካከራሉ፡፡  
ኢህአዴግን ወክለው ለዘንድሮው ምርጫ ከሚቀርቡት የአገሪቷ ከፍተኛ ባለስልጣናት መካከል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድኀኖም በትግራይ፣ ብዛት ምርጫ ክልል አረና መድረክን ወክለው ከሚወዳደሩት ከአቶ ኪዳነ አመነ ጋር ይፎካከራሉ፡፡
በመቀሌ ምርጫ ክልል ዶ/ር አዲስ ዓለም ባሌማ ከአረና መድረክ እጩው ከአቶ ገብሩ አስራት እና ከኢዴፓ እጩ ጋር የሚፎካከሩ ሲሆን የአረና መድረክ እጩዋ ወ/ሮ አረጋሽ አዳነ ለክልል ምክር ቤት በዚሁ ምርጫ ክልል ይወዳደራሉ፡፡ በትግራይ፣ ሰለክላካ ምርጫ ክልል አቶ አባይ ፀሐዬ ኢህአዴግን ወክለው ከአረና መድረኩ እጩ ጋር ይፎካከራሉ ተብሏል፡፡
በደቡብ ክልል ስልጤ ዞን ምርጫ ክልል ደግሞ የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈርጌሳ ከመኢአድና ከሰማያዊ ፓርቲ እጩዎች ጋር የሚወዳደሩ ሲሆን፣ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ፅሕፈት ቤት ዋና ኃላፊ አቶ ሬድዋን ሁሴን ደግሞ ከመድረክ እጩ ጋር ይፎካከራሉ፡፡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል የመንግሥት ተጠሪ የሆኑት ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል በዚሁ ዞን በቅባት ምርጫ ክልል ብቸኛዋ እጩ ተወዳዳሪ ሆነው ይቀርባሉ፡፡
የትምህርት ሚኒስትሩ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በደቡብ ክልል ሲዳማ ዞን በኦሮሬሳ ምርጫ ክልል ከመድረክ እጩ ጋር የሚፎካከሩ ሲሆን የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም በሃዲያ ዞን ሶሮ 02 ምርጫ ክልል ከሰማያዊ እና መድረክ እጩዎች ጋር ይወዳደራሉ፡፡ በ1992 እና በ1997 ዓ.ም በተደረጉ ምርጫዎች አሸንፈው የፓርላማ አባል የነበሩት ታዋቂው ፖለቲከኛ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ መድረክን ወክለው በዚሁ በሃዲያ ዞን ሰቄ 02 ምርጫ ክልል ይወዳደራሉ፡፡ የቤቶችና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሩ አቶ መኩሪያ ኃይሌ፤ በክልሉ ጉራጌ ዞን እዥ 1 ምርጫ ክልል ከሰማያዊና ቅንጅት እጩዎች ጋር ይፎካከራሉ፡፡
በምክትል ጠ/ሚኒስትር ማዕረግ የመልካም አስተዳደር ክላስተር አስተባባሪና የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር ወ/ሮ አስቴር ማሞ ደግሞ በአዲስ አበባ ጨርቆስ ክፍለ ከተማ ይወዳደራሉ፡፡

Published in ዜና

ተቃዋሚ ፓርቲዎች የገንዘብ አቅም ተፈታትኖናል አሉ


ለ5ኛው አገራዊ ምርጫ አዲስ አበባን ጨምሮ በክልል ከተሞች ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቁ  ትላልቅ ቢልቦርዶችና ፖስተሮችን በብዛት በመጠቀም ከተፎካካሪዎቹ ልቆ የታየው ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ፤ በምርጫ ቅስቀሳ በኩል እንደ ዘንድሮም ተሳክቶልኝ አያውቅም ብሏል - ከዕቅዱ 98 በመቶው ውጤታማ እንደሆነ በመግለፅ። ተቃዋሚዎች በበኩላቸው፤ ጠንካራ ቅስቀሳ ማድረጋቸውን ጠቁመው የበጀት እጥረት ያሰቡትን ያህል እንዳይሰሩ እንደተፈታተናቸው ተናግረዋል፡፡
ምርጫ ቦርድ ለምርጫ ማስፈፀሚያ ብሎ ለኢህአዴግ ከ14ሚ. ብር በላይ፣ ለመድረክ 2.2 ሚ. ብር፣ ለኢዴፓ ወደ8 መቶ ሺ ብር፣ ለሰማያዊ ፓርቲ እንዲሁ ወደ 8 መቶ ሺ ብር ገደማ በጀት እንደመደበላቸው ይታወቃል፡፡  
ለተወካዮች ምክር ቤት 165 እጩዎችን በተለያዩ የሃገሪቱ ክልሎች ያቀረበው የኢትዮጵያውያን ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ኢዴፓ)፤ ለምርጫው ወደ 1 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ በጀት ይዞ መነሳቱን ጠቁሞ አብዛኛውን ገንዘብ ለመኪና ላይ ቅስቀሳ፣ ለፖስተሮችና በራሪ ወረቀቶች እንዲሁም ባነሮች ዝግጅት ማዋሉን ገልጿል፡፡
የኢዴፓ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ወንደሰን ተሾመ፤ ፓርቲው እንግሊዝ ሀገር ከሚገኙ ደጋፊዎቹና አባላቱ የተሰበሰበውን 3 መቶ ሺህ ብር እንዲሁም ከምርጫ ቦርድ የተመደበለትን  8 መቶ ሺህ ብር ሙሉ በሙሉ ለምርጫው ማስፈፀሚያ እንደተጠቀመበት አስታውቀዋል፡፡
ኢዴፓ ከ1 ሚሊዮን ኮፒ በላይ በራሪ ወረቀቶች አሳትሞ መበተኑን የጠቆሙት አቶ ወንድወሰን፣ ለእጩ ተወዳዳሪዎች ለእያንዳንዳቸው 300 የሚደርሱ ፖስተሮች አዘጋጅቶ ማሠራጨቱን ገልፀዋል፡፡ ከፖስተሮችና በራሪ ወረቀቶች በተጨማሪ ባነሮችን አሠርቶ በተለያዩ አካባቢዎች ሰቅሎ እንደነበር የተናገሩት አቶ ወንደሰን፤ ባነሮቹ ባልታወቀ ሁኔታ ከቦታቸው መነሣታቸውንና አብዛኞቹ ፖስተሮችም ተቀዳደው መገኘታቸውን ገልፀዋል፡፡
ኢዴፓ የቢል ቦርድ ማስታወቂያ ለመጠቀም ቢያስብም በገንዘብ አቅም ማነስ መተግበር እንዳልቻለም ኃላፊው ይናገራሉ፡፡ “አንድ ቢልቦርድ ለማሰራት ከ70ሺህ ብር በላይ ያስፈልጋል፤ ፓርቲው ደግሞ ይህን የማድረግ አቅም አልነበረውም” ብለዋል አቶ ወንድወሰን፡፡
139 እጩዎችን ለፓርላማ ያቀረበው ሠማያዊ ፓርቲ በበኩሉ፤ ምርጫ ቦርድ ከሠጠው 800ሺህ ብር በተጨማሪ ወደ 1.2 ሚሊዮን ብር ገደማ በጀት ይዞ ቅስቀሳውን እንዳከናወነ ጠቁሟል፡፡ ከመኪና ላይ ቅስቀሳ ባሻገር ባነሮችን፣ ፖስተሮችንና በራሪ ወረቀቶችን እንዲሁም የተወሰኑ ቢልቦርዶችን በመትከል ቅስቀሳ ማድረጉንም የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡
ፓርቲው በተለያዩ ቦታዎች ቢልቦርድ ለመስቀል ሞክሮ ችግር እንደገጠመው የገለፁት ኃላፊው፤ “ከክፍለ ከተማ ፍቃድ አምጡ” የሚሉ ምክንያቶች የታሰበውን ያህል ቢልቦርድ እንዳንሰቅል አድርጎናል ብለዋል፡፡ እንዲያም ሆኖ አዲስ ከተማና ኮተቤ ላይ ብቻ ወደ 10 የሚሆኑ ቢልቦርዶችን ለመትከል እንደቻሉ ሃላፊው ገልፀዋል፡፡
ፓርቲው ለአንድ እጩ እስከ 2ሺህ የሚደርሱ ፖስተሮችን ማሠራጨቱን የጠቆሙት አቶ ዮናታን፤ ወደ 1.5 ሚሊዮን በራሪ ወረቀቶች መበተናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ፓርቲው ለድረ ገጽ የምረጡኝ ቅስቀሳም ከ10ሺህ ብር በላይ ማውጣቱን ሃላፊው ጠቁመዋል፡፡ ለ3 ተከታታይ ቀናት በ8 ተሽከርካሪዎች በአዲስ አበባ ሁሉም ክ/ከተሞች ቀኑን ሙሉ መቀስቀሱንና በክልል ከተሞችም በቂ የመኪና ላይ ቅስቀሳ ማድረጋቸውን አክለው ገልፀዋል፡፡
ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 270 እጩዎችን ያቀረበው መድረክ፤ ከምርጫ ቦርድ ከተሰጠው 2.2 ሚሊዮን ብር ውስጥ ወደ 700 ሺህ ብር ገደማ ለመኪና ላይ ቅስቀሳዎች ማዋሉን ጠቁሟል፡፡ የቀረውን ገንዘብ ለምርጫ ታዛቢዎች የውሎ አበል በነፍስ ወከፍ 50 ብር እንዲከፋፈል መደረጉን የመድረክ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጥላሁን እንዳሻው ገልፀዋል፡፡
“መድረክ ሊሰራ ካሰበው አንፃር የገንዘብ አቅሙ የጠብታ ያህል ነው” ያሉት ኃላፊው፤ የገንዘብ ችግሩን ለመቅረፍ እያንዳንዱ እጩ የራሱን ወጪ በግሉ መሸፈኑን ተናግረዋል፡፡
ፓርቲው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ በራሪ ወረቀቶች ማሰራጨቱን የጠቆሙት ኃላፊው፤ በኦሮሚያ ክልል ብቻ በኦፌኮ አማካኝነት ወደ 5 ሚሊዮን በራሪ ወረቀቶች ተበትነዋል ብለዋል፡፡ በሌሎች ክልሎችም በሚሊዮን የሚቆጠሩ የቅስቀሳ በራሪ ወረቀቶች መሰራጨታቸውን ተናግረዋል፡፡
“መድረክ ያሰበውን ያህል ቅስቀሳ እንዳያደርግ የፋይናንስ እጥረት ተግዳሮት ሆኖበታል” ያሉት አቶ ጥላሁን፤ በዚህም ምክንያት ቢልቦርድ ማዘጋጀት አልተቻለም ብለዋል፡፡
501 እጩዎችን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበው ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ በበኩሉ፤ እስካሁን ለቅስቀሳ ስራ ያወጣው አጠቃላይ ወጪ በትክክል እንደማይታወቅ ጠቁሞ ፓርቲው ከምርጫ ቦርድ የተመደበለትን 14 ሚሊዮን ብር ገደማ፣ ከአባላት ከተሰበሰቡ መዋጮዎች ጋር በማጣመር ስኬታማ የቅስቀሳ ስራ መስራቱን አስታውቋል፡፡
በ2002 ምርጫ ከቅስቀሳ ዕቅዳችን 70 በመቶ ብቻ ነበር ያሳነካው ያሉት የኢህአዴግ ፅ/ቤት የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ደስታ ተስፋው በዘንድሮ ምርጫ 98 በመቶ ውጤታማ ቅስቀሳ አድርገናል ብለዋል፡፡ ኢህአዴግ ቢልቦርዶችን፣ በየአካባቢው የሚደረጉ ህዝባዊ ስብሰባዎችን፣ ፖስተሮችን እንዲሁም፣ የመኪና ላይ ቅስቀሳዎችን በማከናወን ሁሉንም አማራጮች አሟጦ መጠቀሙንና ለህዝቡ በበቂ ሁኔታ ተደራሽ መሆኑን አቶ ደስታው አክለው ገልጸዋል፡፡ 

Published in ዜና

ምርጫ ቦርድ በህገወጦች ላይ የከፋ እርምጃ እወስዳለሁ ብሏል
ሞባይል ስልክ ይዞ መግባት አይፈቀድም

ነገ በሚካሄደው 5ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ላይ በየምርጫ ጣቢያዎቹ ጥብቅ ፍተሻና ጥበቃ እንደሚደረግ የጠቆመው ምርጫ ቦርድ፤ ከህግና ሥርዓት ውጪ ሆነው በተገኙ ወገኖች ላይ ጥብቅ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታወቀ፡፡ መራጮች ወደ ምርጫ ጣቢያዎች በሚሄዱበት ወቅት ከምርጫ ካርዳቸውና ከመታወቂያ ወረቀታቸው ሌላ ምንም አይነት ነገሮችን ይዘው መግባት እንደማይፈቀድላቸውም ተገልጿል፡፡
የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ በቃና ከትናንት በስቲያ በሒልተን ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ ምርጫው ሠላማዊ በሆነ መንገድ እንዲካሄድ ለማድረግ የሚያስችል ቅድመ - ዝግጅት ተጠናቋል፡፡ መራጮች ወደ ምርጫ ጣቢያ ሲሄዱ ሞባይል ስልካቸውንም ሆነ ሌላ ምንም ዓይነት መሣሪያዎችን ይዘው መግባት አይፈቀድላቸውም፡፡
የምርጫው በሰላማዊ መንገድ መጠናቀቅ የቦርዱ ኃላፊነት መሆኑን ያስገነዘቡት ፕሮፌሰር መርጋ፤ ይህንን ሁኔታ ለማስጠበቅም ሠላማዊ የምርጫ ሂደትን ለማደፍረስ በሚንቀሳቀሱ ወገኖች ላይ ቦርዱ የሚወስደው እርምጃ የከፋ ይሆናል ብለዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ በቂ ዝግጅት ተደርጓል ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡

Published in ዜና

አሁን የወጣቱ ልብና አዕምሮ ከአገር ውጭ ነው
ከፍተኛው የስደት መንስኤ የተሻለ ህይወት ፍለጋ ነው (ILO)
“በአገር ቤት ሰርቶ መለወጥ ይቻላል የሚለው ዲስኩር ለውጥ አያመጣም”
    አሊ ሃሰን፤ በቅርቡ በሜዲትራኒያን ባህር ህይወታቸውን ያጡት 8 የመርካቶ አባኮራን ሠፈር ልጆች አብሮ አደግ ነው፡፡ መጋቢት 1 ቀን 2007 ዓ.ም “በሰላም ያግባችሁ” ብሎ የሸኛቸው አብሮ አደጐቹ ድንገት የሞታቸውን መርዶ ሲሰማ ክፉኛ ከመደንገጡ የተነሳ ማመን አቅቶት እንደነበር ይናገራል፡፡ “ቤተሰቦቻቸው በድህነት ያሳደጓቸው አብሮ አደጐቼ፣ ያልፍልናል ብለው ነው ህይወታቸው ያለፈው” የሚለው የ25 አመቱ አሊ፤ እነሱ ከወራት በፊት ወደ ሊቢያ ለመሻገር የሱዳን ቪዛ ሲሰጣቸው በቂ ገንዘብ በእጁ ላይ ባለመኖሩ ተነጥሏቸው እንደቀረና ገንዘብ ሲያገኝ እንደሚቀላቀላቸው ቃል ገብቶላቸው መለያየታቸውን ያስታውሳል፡፡ አሁን አሊ ወደ ሱዳን የሚያስገባውን የ2 ወር የቱሪስት ቪዛ ለማግኘት እየተሯሯጠ ሲሆን በቅርቡ ተጓዥ ነኝ ብሏል - ለአዲስ አድማስ፡፡ “ይህን ሁሉ ሞትና አሰቃቂ ነገር እየሠማህ እንዴት ትሄዳለህ?” በሚል ለቀረበለት
ጥያቄ ሲመልስ፤ “እነሱ እድላቸውን ሞክረው አልተሳካላቸውም፤ እኔም እድሌን ልሞክር” ነው ያለው፡፡ በሃገር ቤት ሠርቶ መለወጥ ይቻላል፤ አሹቅ በልተን በእናቶቻችን ጉያ ውስጥ መኖር ምናምን  የሚባለው ለኔ ትርጉም የለውም” የሚለው አሊ፤ እዚህ ሀገር ተቀምጬ እስከ መቼ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ እመራለሁ ሲልም”  ይጠይቃል፡፡ ከሊስትሮ ጀምሮ አነስተኛ ሥራዎችን መስራቱን የሚናገረው ወጣቱ፤ ከ6 አመት በላይ የተለያዩ ተባራሪ የንግድ ስራዎችን ቢሰራም ከቤተሰብ ጥገኝነት መላቀቅ እንዳቃተው ይናገራል፡፡ ከእናቱና
ከሁለት እህቶቹ ጋር እንደሚኖር የጠቆመው አሊ፤ ከ3 አመት በፊት አባቱ መሞታቸውን ተከትሎ እህቶቹን የማስተማርና ወላጅ እናቱን የመጦር ሃላፊነት  እንደወደቀበት ይናገራል፡፡ ቤተሰቤ ፆም እንዳያድር ከጠዋቱ 12 ሰአት ጀምሮ እስከ ምሽት 2 ሰዓትና 3 ሰዓት ድረስ የተለያዩ ተባራሪ ስራዎችን ስሰራ ብውልም በቀን ከ60 እና 70 ብር በላይ ገቢ አላገኝም ይላል - ወጣቱ በምሬት። “በ70 ብር ምን ልታደርግበት ነው? ቁርስና ራትን እንተወውና ምሣ እንኳ ልብላ ቢባል ከ20 ብር በታች የሚሸጥ ምግብ የለም” የሚለው ወጣቱ፤ በቀን የሚያገኛትን 60 እና 70 ብር እንደምንም አብቃቅቶ ቤተሰቡን ከረሃብ እንደሚታደግ ነው የገለፀው፡፡ ግን በዚህ ሁኔታ እስከ መቼ እቀጥላለሁ በማለት ይጠይቃል፡፡ እናም ቀድሞ በጣሊያን አድርጐ እንግሊዝ ሃገር የገባ አብሮ አደጉ አሁን እስከ ሱዳን ሊያደርሰው የሚችል ገንዘብ እንደላከለትና በዚያም አስፈላጊውን የጉዞ ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተናግሯል፡፡ ባለፈው ሳምንት የ7ቱን አብሮ አደግ ጓደኞቻቸውን ሞት የተረዱት የአባኮራን ሰፈር ወጣቶች፤ ክፉኛ አዝነው የነበረ ቢሆንም አብዛኞቹ ግን ከአገር የመውጣት ከፍተኛ ጉጉት እንዳላቸው ገልፀውልናል፡፡ “እዚህ ሃገር 24 ሰዓት ቢሠራ ጠብ የሚል ነገር የለም” የሚሉት ወጣቶቹ፤ ከሃገር ከተወጣ ግን በተጨባጭ መለወጥ እንደሚቻል ከዚህ ቀደም የሄዱ ጓደኞቻቸውን በምሳሌነት እየጠቀሱ ያስረዳሉ፡፡ በሳሪስ አቦ አካባቢ በሊስትሮ ስራ የተሠማራው ጋዲሣ፤ ከትውልድ ሀገሩ አምቦ ወደ አዲስ አበባ የመጣው በመዲናይቱ ሰርቶ ለመለወጥ የሚል ዓላማ አንግቦ ሳይሆን ፓስፖርት ለማውጣት ነው፡፡ ፓስፖርቱን ከ4 ወራት በፊት ማውጣቱን የሚናገረው ወጣቱ፤ አሁን ደግሞ የሱዳን ቪዛ ለማግኘት
እየጣረ መሆኑን ይገልፃል፡፡ “በአይኤስ አሸባሪ ቡድን ስለታረዱትም ሆነ በሜዲትራኒያን ባህር ስለሰመጡት ሰዎች በሚገባ ሰምቻለሁ፤ መስቀል አደባባይ አይኤስን ለማውገዝ በተጠራው ሠልፍ ላይም ተሳትፌያለሁ፤ ግን ወደ አውሮፓ በየትኛውም መንገድ የመሄድ ሃሳቤን አልሰረዝኩም። ምክንያቱም እዚህ ጠብ የሚል ነገር የለም፤ ጓደኞቼ የደረሱበት ደረጃ መድረስ እፈልጋለሁ” ሲል ዓላማውን ገልጿል፡፡ ከቴክኒክና ሙያ በአውቶ ኤሌክትሪሲቲ በሠርተፍኬት መመረቁን የሚናገረው ጋዲሳ፤ እንግሊዝ ወይም ፈረንሳይ ቢገባ በተማረው ሙያ ስራ ሊያገኝ እንደሚችል ተስፋ ያደርጋል፡፡ ከሁለት አመት በፊት በጣሊያን አድርገው እንግሊዝ የገቡ ሁለት አብሮ አደጐቹ በተማሩበት የመካኒክ ዘርፍ በጋራዥ ውስጥ ተቀጥረው እየሠሩ መሆኑን እንደነገሩት የጠቀሰው ወጣቱ፤ ጓደኞቹ በሁለት አመት ጊዜ ውስጥም ለቤተሰቦቻቸው ገንዘብ መላክ እንደጀመሩ ይናገራል፡፡ የተወሰነ ለጉዞው ጉዳይ ማስፈፀሚያ የሚሆን ገንዘብም ለእርሱ እንደላኩለት ገልጿል፡፡ እናትና አባቱ ከሞቱ በኋላ ከሶስት ወንድሞቹ ጋር የተካፈላትን ውርስ ሸጦ ለጉዞው የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለማሟላት ማሰቡንም ይናገራል፡፡ በጉዞህ ላይ አደጋ ቢያጋጥምህስ? በሚል ሲጠየቅ፤ “እሱ የእድል ጉዳይ ነው፤ እድሌን እሞክራለሁ” ባይ ነው፡፡ በሌላ በኩል በ2006 ዓ.ም ከሣኡዲ በተባረሩ ኢትዮጵያውያን ዙሪያ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ የሚንቀሳቀሰው የክርስቲያን ተራድኦ በጎ አድራጎት ድርጅት (CCRDA) ተመላሾቹ ስላሉበት ሁኔታ የሚገመግም የጥናት ሰነድ ሰሞኑን ይፋ ያደረገ ሲሆን ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው የሣውዲ ተመላሾች ተመልሰው ከሃገር መሰደዳቸው ተጠቁሟል፡፡ በፕሮግራሙ ላይ ተጋባዥ ከነበሩ ጥቂት ተመላሾች መካከልም ሁለት ወጣቶች አሁን ያሉበትን ሁኔታ ለተሰብሳቢው ገልፀው ነበር፡፡ ሣውዲ አረቢያ በሰው ቤት ለሁለት አመት ተቀጥራ ትሠራ እንደነበር የገለፀችው በ20ዎቹ መጀመሪያ ላይ የምትገኘው ዘይነብ፤ ለሁለት አመት የሠራችበት ደሞዟን ተከልክላና ተባራ ጐዳና ወድቃ የነበረ ባዶ እጇን ወደ ሀገሯ እንደተመለሰችም ትናገራለች፡፡ በወር 700 ሪያል እንደሚከፈላት ተዋውላ ትሠራ እንደነበር የገለፀችው ዘይነብ፤ ሣውዲ ለሁለት አመታት የደከመችበት ወደ 16ሺህ ሪያል ገደማ ሣይከፈላት ባዶ እጇን ከተመለሰች በኋላ አንድ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት አስጠግቷት ለአንድ አመት እንደተንከባከባትና ከአንድ አመት በኋላ በምግብ ስራ ሙያ አሠልጥኗት ከ8 ሺህ ብር በላይ አውጥቶ የማብሰያ ማሽን ገዝቶ በመስጠት “በዚህ ስሪና ራስሽን ለውጪ” እንዳላት ተናግራለች፡፡ ይሁን እንጂ ዘይነብ ማሽኑን ታቅፎ ከመቀመጥ ውጪ ሥራ ልትሠራበትና ህይወቷን ልታሻሽልበት አልቻለችም፡፡ “መንግስት የመስሪያ ቦታ ሊሠጠኝ ፍቃደኛ ባለመሆኑና የንግድ መነሻ የሚሆን ገንዘብም ማግኘት ባለመቻሌ ዝም ብዬ ተቀምጬአለሁ” ብላለች፡፡ “በወጣትነቴ የሰው ጥገኛ ሆኜ መኖሬ ያሳስበኛል” ስትል የምታማርረው ዘይነብ፤ በሳውዲ ብዙ ግፍና መከራ የደረሰባት ቢሆንም አሁንም እድሉን ብታገኝ ወደዚያው አሊያም ወደ ሌላ ሀገር ከመሄድ ወደ ኋላ እንደማትል ገልፃለች፡፡ ሀገር ቤት ባለው ሁኔታ ተስፋ መቁረጧንም ወጣቷ በምሬት አስረድታለች፡፡
ሣውዲ እያለች ልጆቿን ጥሩ ትምህርት ቤት ታስተምር፣ ቤተሰቦቿንም በሚገባ ትረዳ እንደነበር ያወሳችው ሌላኛው ወጣት በበኩሏ፤ በአሁን ሰአት ከልጆቿ ጋር የቤተሰቦቿ ጥገኞች ለመሆን እንደተገደዱ ትገልፃለች፡፡
“በቴሌቪዥን ስጠየቅ በሃገር ቤት ሠርቶ መለወጥ ይቻላል ብዬ ነበር” ያለችው ወጣቷ፤ አሁን ግን ይሄን የማለት ድፍረት የለኝም ብላለች፡፡ መንግስት አደራጅቶና ብድር አመቻችቶ መለስተኛ የንግድ ስራ ከጓደኞቿ ጋር መጀመሯን እንዲሁም እዳቸውንም መክፈል መጀመራቸውን የጠቆመችው ወጣቷ፤ እዳቸውን እንኳ ሳይጨርሱ የ5ሺህ ብር ግብር እዳ አለባችሁ እንደተባሉ ተናግራለች፡፡ “በዚህ ሁኔታ እንዴት ነው ተመላሾች ሊቋቋሙና በሀገራቸው ሠርተው ሊለወጡ የሚችሉት?” ስትልም ትጠይቃለች፡፡በቤተሰቦቿ እጅ ላይ ተመልሣ መውደቋ ክፉኛ እንደሚያሳስባት የገለፀችው ወጣቷ፤ የቤተሰቦቿንም ሆነ የልጆቿን ህይወት ቀድሞ ወደነበረበት ለመመለስ የግዴታ ወደ ውጭ ወጥታ መስራት እንዳለባት ማመኗንና ለመሄድ አጋጣሚዎችን እየጠበቀች መሆኑን በምሬት ተናግራለች፡፡ በመድረኩ ላይ የታደሙት የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካይ በበኩላቸው፤ መንግስት ስደቱን እያባባሱ ነው በሚላቸው ህገ ወጥ ደላሎች ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን እንዲሁም ዜጐች በሀገራቸው ሰርተው የሚለወጡበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ከወትሮው በተለየ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከመንግስት ጐን ሌሎች ባለድርሻ አካላትና ህብረተሰቡ መሣተፍ እንዳለበትም ተወካዩ አሳስበዋል፡፡ መንግሥታዊ ባልሆነ ድርጅት ውስጥ የማህበረሰብ ጥናት (ሶሺዮሎጂ) ባለሙያ በመሆን የሚሰሩት ዶ/ር ተካልኝ አባተ በበኩላቸው፤ አሁን ከመንግስት እየቀረቡ ያሉት ምክንያቶችና የመፍትሔ ሃሳቦች በቂም፤ አሣማኝም አይደሉም ይላሉ፡፡ “በሃገር ቤት ሠርቶ መለወጥ ይቻላል የሚለው የቀን ተቀን ዲስኩር አሠልቺ ከመሆን ያለፈ የግንዛቤ ለውጥ አያመጣም፣ መንግስት የፖሊሲ አማራጮቹን በሚገባ ማየትና መገምገም ይገባዋል” ብለዋል ምሁሩ፡፡ የማህበረሰብ ጥናት ባለሙያዎችን ጨምሮ የተለያዩ ምሁራን በጉዳዩ ላይ ጥልቀት ያለው ጥናትና ምርምር እንዲያደርጉም መንግስት መጋበዝ
እንዳለበት ዶ/ሩ ይመክራሉ፡፡ አለማቀፉ የሰራተኞች ድርጅት (ILO) ከግንቦት እስከ ሐምሌ 2014 ወደ አገራቸው በተመለሱ ስደተኞች ላይ ያደረገው ጥናት ውጤት እንደሚያመለክተው፤ ለስደታቸው መንስኤ ከሆኑ ምክንያቶች ከፍተኛውን ደረጃ የሚይዘው የተሻለ ህይወትን ፍለጋ የሚደረገው ስደት ነው፡፡ በህገወጥ ደላሎች ጉትጐታ አማካኝነት የሚደረገው ስደት እጅግ አነስተኛ ቁጥር ያለው መሆኑን አመልክቷል፡፡ እንደ ILO ሪፖርት፤ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ከስደት ተመላሾች ዳግም መሰደድ የሚፈልጉ ናቸው፡፡




የመድረክ ግንባር መስራች ፓርቲ የሆነው “አረና ትግራይ ለሉአላዊነትና ለዲሞክራሲ” በትግራይ ክልል ዋነኛው የገዢው ህውሓት ፓርቲ ተፎካካሪ ሆኖ በመጪው ሳምንት ምርጫ ይወዳደራል። አረና በአጠቃላይ ለምርጫው እያደረገ ስላለው እንቅስቃሴና ዝግጅት እንዲሁም ከምርጫው ምን ውጤት እንደሚጠብቅ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ የፓርቲውን ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ጎይቶም ጸጋን አነጋግሯል፡፡


“አረና” ለዘንድሮ ምርጫ በትግራይ ክልል ምን ያህል እጩዎች አቅርቧል?
ፓርቲው በክልሉ በ38ቱም የምርጫ ክልሎች ለመወዳደር እየሰራ የነበረ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች እጩዎቹ ተቀንሰውበት አሁን 28 ናቸው ለተወካዮች ም/ቤት የሚወዳደሩት፡፡ ይህም ሆኖ ግን የክልሉን ህዝብ በመንግስትነት ለመወከል የሚያበቃ የእጩ ቁጥር ነው ያለን፡፡
ለምርጫው እያደረጋችሁት ያለው የመጨረሻ ዝግጅት ምን ይመስላል?
 በአጠቃላይ ቅስቀሳዎችን በተጠናከረ መልኩ እያካሄድን ነው፡፡ ህዝባዊ ስብሰባዎችንም እያደረግን ነው፡፡ እስካሁን በመቀሌ ብቻ ነው ያልተሳካው፡፡ እሱንም ቢሆን ዛሬ (ቅዳሜ) እናደርጋለን፡፡ በየቦታው ያሉ እጩዎችና አስተባባሪዎች በየአቅጣጫው ቅስቀሳቸውን እያደረጉ ነው፡፡ ከምርጫ ቦርድ የተመደበልንን በጀትም ሆነ ሌሎች የገንዘብ አቅሞቻችንን ተጠቅመን በ13 ያህል መኪኖች የመጨረሻውን ቅስቀሳ ለማድረግ በዝግጅት ላይ እንገኛለን፡፡
አረና ለክልል ምክር ቤት ያቀረባቸው እጩዎች ብዛት የትግራይ ክልል መንግስትን ለመመስረት የሚያስችል ነው?
በክልሉ አጠቃላይ ወደ 152 እጩዎች ናቸው የሚያስፈልጉት፡፡ እኛ ደግሞ ወደ 77 ያህል አቅርበናል፡፡ እንግዲህ በውድድሩ አብላጫ ቁጥር ለመያዝ ነው ያሰብነው፡፡ መንግሥት እንመሰርታለን ብለን ነው እየሰራን ያለነው፡፡ ከግማሽ በላይ የምርጫ ክልሎችን ካሸነፍን መንግስት የማንሆንበት ምክንያት የለም፡፡
በገዥው ፓርቲ በኩል አረና ከግማሽ በላይ ለማሸነፍ የሚያስችል እጩ እንዲያቀርብ አልተፈለገም ነበር፡፡ የእጩዎች ቁጥር የተለያዩ ምክንያቶችን እያቀረቡ ነው እንዲቀነስብን የተደረገው፡፡
በየትኞቹ አካባቢዎች ነው በእርግጠኝነት ልናሸንፍ እንችላለን ብላችሁ የምታስቡት?
ለይተን የምናስቀምጠው አካባቢ የለንም። አጠቃላይ እንቅስቃሴ ነው እያደረግን ያለነው። እየተወዳደርን ያለነው አሸንፈን ፖሊሲያችንን በሃገራችን እናስፈፅማለን በሚል እምነት ነው። ዓላማችን ሁለት ወይም ሶስት ወንበር ብቻ አግኝቶ ለመቀመጥ አይደለም፡፡ በአጠቃላይ በተወዳደርንባቸው ቦታዎች አብላጫውን ውጤት ይዘን እንወጣለን የሚል እምነት ነው ያለን፡፡
ከእስካሁኑ እንቅስቃሴያችሁ አንፃር ከምርጫው የምትጠብቁት ውጤት ምንድን ነው?
እንግዲህ በጥሩ ሁኔታ እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ መታወቅ ያለበት ግን የኛ እንቅስቃሴ ብቻ አይደለም ውጤታማ ሊያደርገን የሚችለው፡፡ የህዝቡም ሚና አለ፡፡ አቅማችን በፈቀደ መጠን እንቅፋቶችን ተቋቁመን ለመሄድ እየሞከርን ነው፡፡ ጠንካራ ስራም እየሰራን ነው፡፡ ነገር ግን ከዚህ ምርጫ ተአምር አንጠብቅም፡፡ በጣም ከባድ ሊሆንም ይችላል። ምክንያቱም ገዥው ፓርቲ ህዝቡ ድምፁን እንዲሰጥ ነፃ ያደርገዋል የሚል እምነት የለንም፡፡ የሰራነው ነገር በቂ ነው ብለው ስለሚያስቡ መንገዱን ሁሉ ሊዘጉት ይችላሉ፡፡ ታዛቢዎችን ማስፈራራት ሊኖር ይችላል። ከዚህ አንፃር ካለፈው ምርጫም ተነስተን በነዚህ ጫናዎች የተነሳ አሁንም ኢህአዴግ ሊያሸንፍ ይችላል የሚል ስጋት ነው ያለኝ። ምክንያቱም ታዛቢ ጫና ከተደረገበት ምርጫው እንዴት ውጤት ሊገኝበት ይችላል፡፡ ያም ሆነ ይህ እኛ ተስፋ አንቆርጥም። በዚያች ቀን እንኳ ምርጫው ነፃና ፍትሃዊ ከሆነ መንግስት የማንሆንበት ምክንያት የለም፡፡ ህዝቡ እኮ ከኢህአዴግ ጋር አይደለም፡፡ በእርግጥ እነሱ ያን ቀን ምርጫውን ያለ ታዛቢ አፍነው ከያዙት አሁን ካላቸው የ99.6 በመቶ ውጤት ወደ 100 በመቶ ሊያመጡት ይችላሉ፡፡
እናንተ ግን ለምርጫው የሚጠበቅብንን ስራ ሰርተናል፤ በቂ ዝግጅት አድርገናል የሚል እምነት አላችሁ?
የኛም ስራ መቶ በመቶ ውጤታማ ነው ለማለት አይቻልም። ጉድለቶች አለብን፡፡ ግን ምርጫው የሚወሰነው በኛ እንቅስቃሴ ብቻ አይደለም፤ የህዝቡ ፍላጎት ወሳኝ ነው፡፡ በጣም ብዙ ክፍተቶች እንዳሉብን እናውቃለን፤ በቀጣይ መማሪያ ይሆኑናል።
ከምርጫ 2002 እና ከአሁኑ ምርጫ “አረና” ይበልጥ ተጠናክሬ ቀርቤአለሁ የሚለው በየትኛው ነው?
ባለፈው ምርጫ የእጩዎች ቁጥር ይበዛል፡፡ የአሁኑ በተለያዩ ምክንያቶች ቀንሷል፡፡ በእጩ ቁጥር ሲታይ ባለፈው ምርጫ የተሻለ ቁጥር ያቀረብን ቢሆንም በአጠቃላይ እንቅስቃሴው ግን በአሁኑ ጠንካራ ሆነናል፡፡ አረና እየተዳከመ ነው ማለት አይቻልም፡፡ በ2002 ምርጫ ቅስቀሳና ስብሰባዎችን በማድረግ ጥሩ የነበርን ቢሆንም በአሁኑ በተለያዩ ምክንያቶች ትንሽ መስተካከል ያለባቸው ነገሮች አሉ። ዞሮ ዞሮ በኛ እንቅስቃሴ ብቻ ሳይሆን በህዝቡም ይወሰናል፡፡
እናንተ ከተፎካካሪያችሁ የበለጠ የህዝብ ተቀባይነትና ድጋፍ አለን ብላችሁ ታምናላችሁ?
ምንም ጥርጥር የለውም፤ ተቀባይነት አለን። ለዚያ አይደለም እንዴ ፈርተው እያሰሩን ያሉት። ይሄንንማ ህውሓቶችም በሚገባ ያውቃሉ፡፡ በትግራይ ስብሰባና ሰልፍ የሚከለክሉበት ምክንያት እኮ  ስለሚፈሩንና ተቀባይነት እንዳለን ስለሚያውቁ ነው፡፡
በትግራይ ከህውሓት ውጪ ጠንካራ ተቀናቃኝ የምትሉት ፓርቲ አለ?
ዋነኛው ተቀናቃኛችን ህውሓት ነው፡፡ እሱም ዋነኛ የሆነው በጉልበት ነው፡፡ ሌላ ፓርቲ ግን ያለ አይመስለኝም፡፡ ከተቃዋሚዎች የተሻለ እጩ ያቀረበው አረና ነው፡፡ ፉክክሩ በዋናነት በህውሓትና በአረና መካከል ነው፡፡

Page 7 of 19