ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ልጅ ገመድ ዝላይ ከሚዘሉ ልጆች ጋር ሊጫወት ከቤቱ ይወጣል፡፡ አባቱ ከፎቅ ሆኖ የስተውለዋል፡፡
አባትየው የሚያየውን ለማመን አልቻለም፡፡
ልጁ ገመዱን የሚያዞሩትን ልጆች፤
“እኔንም ገመድ ዝላይ አጫውቱኝ?” ሲል ጠየቃቸው፡፡
“እሺ ዝለል” አሉት፡፡
ልጁ መዝለል ጀመረ፡፡
ልጆቹም ገመዱን ማዞር ቀጠሉ፡፡
አስገራሚው ነገር ግን ልጁ የሚዘለው ሌላ ቦታ ነው፤ ልጆቹ ገመዱን የሚያዞሩት ሌላ ቦታ ነው፡፡ ልጁ መዝለውን ቀጠለ፡፡
ልጆቹ ይቀልዱበታል፡፡ ይስቁበታል፡፡ እሱ መዝለሉን ቀጥሏል፡፡ አይፎርሽም፡፡ ደስ ብሎታል፡፡
አባትዬው በሁኔታው አዝኖ ከፎቅ ወርዶ መጥቶ ልጁን መዝለሉን አስቆመውና ወደቤት አስገባው፡፡ ልብሱን አስቀይሮ ወደ ሐኪም ቤት ወሰደው፡፡ ሐኪሙም፤
“ምን ችግር ገጠማችሁ፤ ምን ልርዳችሁ?” አለ
አባት ልጁ ሲጫወት ምን ያደርግ እንደነበረ ገለጠለትና “ምናልባት ልጄ አንድ ዓይነት የአዕምሮ ወይም አካላዊ ችግር እንዳይኖርበት ብዬ ነው” ሲል አስረዳ፡፡
ሐኪሙ ለልጁ ብዙ ምርመራ ካደረገለት በኋላ የዓይን ችግር እንዳለበት አረጋገጠና መነፅር አዘዘለት፡፡
ልጁ መነፅር ተገዛለት፡፡ መነፅሩን አድርጐ ወደ ገመድ ዝላይ ጨዋታው ሄደ፡፡
አሁን በትክክል ገመዱ ማህል ገባ፡፡ አዞሩለት፡፡ በትክክል መዝለል ጀመረ፡፡ አንዳንዴ ነው እንጂ አልፎረሸም፡፡ ቀጠለ ዝላዩን!!
*    *    *
ገመዱ በሌለበት የምንዘል አያሌ ነን፡፡ ሐኪም ያላየ ዐይን ያለን በርካታ ነን፡፡ በትክክል እንዳልዘለልን እያዩ፣ እየታዘቡ፤ እየሳቁ፣ እየተሳለቁ የሚያዩንም ብዙ ናቸው፡፡ ገመድ ማዞሩን እንደስራ ቆጥረው ዕድሜ - ልካቸውን ቢሮክራሲው ውስጥ የሚኖሩም የትየለሌ ናቸው፡፡ እንደ መልካም አባት ያለ መልካም መሪ፣ መልካም ኃላፊ፣ መልካም አለቃ የልጁን ችግር ተረድቶ ወደሀኪም ዘንድ ይወስዳል፡፡ ለችግሩ መፍትሔ ይፈጥራል፡፡
የሚስቁ፣ የሚሳለቁትን ሁሉ ኩም ያደርጋቸዋል፡፡ “የሚሠሩትን አያውቁትምና ይቅር በላቸው” ይላቸዋል፡፡
በገመድ ዝላይ መፎረሽ እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ ግን የፉረሻውን ቁጥር መቀነስ ይቻላል። ከገመዱ ውጪ መዝለል ከጨዋታው ውጪ ነው ቢባልም፣ ልምዱ ግን ቀላል አደለም ብሎ መከራከርም ይቻላል፡፡ የልጁ የዕይታ ችግር (Sight problem) የሁላችንም ችግር ቢሆንስ ብለን ማሰብ አለብን (myopic or farsighted እንዲል ፈረንጅ - የአፍንጫ ሥር ማየትና አርቆ - ማስተዋል እንደማለት)፡፡ ማመን ነው እንጂ አለማመን ምን ያቅታል፤ ይላል አንድ ፀሐፊ
ዕውነትን መሠረት ካደረግን ውሸትን መናቅ ቀላል ነው፡፡
“ሐሰተኞች ሰዎች ቢምሉ ቢገዘቱ ነገራቸውን በአየር ላይ በሚበሩና ፍለጋቸው በማይገኝ ዎፎች መስለው፡፡ ለመብረራቸው ፍለጋ እንደሌለው፤ ሐሰተኞች ሰዎች ለሚናገሩትም ነገር ሥር መሠረት የለውምና” ይላሉ የአገራችን ፈላስፎች፡፡
በነባራዊነትና በህሊናዊነት አንፃር ከተመለከትን የማይዋሹ ነገሮችን መዋሸት ጅልነት ነው። አንድ አዛውንት “እንዴት ፖለቲከኛ ለመሆን ቻሉ?” ተብለው ቢጠየቁ፤ “የዕውቀት ማነስ ነው ፖለቲከኛ ያደረገኝ!” አሉ፤ አሉ፡፡ “አንተስ የአገራችን ምሁር ያደረገህ ምንድነው?” ብለው አዛውንቱ ቢጠይቁት “ያው መማሬ ይመስለኛል ሌላ ሰበብ አይሰማኝም” አለ ምሁሩ፡፡ አዛውንቱም “አንተን ምሁር ያረገህ ደሞ ምን መሰለህ?...የዕውነት ማነስ!” አገራችን ከእኒህ አዛውንት ዕሳቤ ውጪ አይደለችም፡፡ የዕውነትና የዕውቀት ማነስ ፖለቲከኛም፣ ምሁርም አድርጐናል፡፡ ያወቀ ያውቀዋል። ያለቦታው ገመድ መዝለልም ክህሎት ይሆናል፡፡ በዛሬ ግንቦት ሃያ ማግስት ሆነን፣ “አንጋረ - ፈላስፋ” የሚለው መፅሐፍ የሚለንን ብናስብ ፀጋ ነውና እነሆ:-
“ዕውነትን መናገር፣ በሐሰት ከመማል መራቅ፣ ሰውን ፊትን አብሮቶ መቀበል፣ እንግዶችን አክብሮ መቀበል፣ በጐ ሥራ መሥራት፣ ጐረቤትን ተጠንቅቆ መያዝ፣ Uዕቢትን አለማድረግ፣ ሁልጊዜ ሰውን ማክበር፣ ትህትናን ማዘውተር፣ አንደበትን ክፉ ከመናገር መግታት፣ ቀናውን ነገር መናገር፣ ለሁሉም በቅንነት መመለስ፣ የወንድምን ኃጢያት መሠወር፣ ሽንገላን (ምሎ - መክዳትን) መተው፣ ጉባዔ ፊት ጮክ ብሎ አለመናገር” እነዚህን ቃላቶች ሁሉ ገንዘብ ያደረገ ሰው በዕውነት አዋቂ ነው፣ ዐዋቂ ይባላል”
ትርጓሜውም፤ ባጭሩ፤
“ዕምነትህን አትካድ፡፡ ከጐረቤት ጠንቅ መጠበቅ፡፡ የፖለቲካ አቀባበልና አያያዝን ማወቅ። በፓርላማ ፊት አለመፎከር፡፡ መሬት ላይ ምን እንደሚጠብቀን አናውቅምና፡፡” ይሄ የወቅቱ መልዕክት ይሁነን፡፡
ነብሳቸውን ይማረውና አባ ጳውሎስ ረዥም ፍትሐተ - ፀሎት ያደረጉለት፤ ነብሱን ይማረውና የአድዋው ደራሲ ስብሃት ገ/እግዚአብሔር፤
“ግንቦት ሃያን እንዴት ታየዋለህ?” ሲባል፤
“እንደሰኔ ሃያ” ያለው አይረሳንም፡፡
ድሎቻችንን አንረሳም፡፡ ሌላ ድል ለማስመዝገብ የቀደሙት ድሎች ከትውስታነት ባሻገር አገልግሎት የላቸውም፤ እንደ አድዋ ድል ሁሉ፡፡ ወሳኙ የዛሬ ዝግጁነታችን ነው፡፡ የዛሬ ማንነታችን ነው፡፡ የሚከፈለን ካሣም በወቅቱ ፍሬ ነበረ፡፡ ወደ ሰላማዊ ትግል ስንዘዋወር ምርቱ ለሌላ ዕድገት መስፈንጠሪያ - ድልድይ (Spring Board) ሆኗል፡፡ ስለዚህም ጊዜው ብዙ መናገሪያ ሳይሆን ማድረጊያ ሆኗል ማለት ነው፡፡ መስከረም ሁለትን ከግንቦት ሃያ የሚለየው ይሄ ነው፡፡ ድፋትና ቅናት ነው በያሬድኛ፡፡ ትንሽ ምላስ እና ብዙ እጅ እንደማለት ነው፡፡ ይሄ ለተቃዋሚም፣ ለአልተቃዋሚም፣ ለአዘቦት - ሰውም ዕውነት ነው፡፡
ለዚህ ነው ከምዕተ - አመታት በፊት የነበሩ ፈላስፎቻችን፤ “ድምፅን ከፍ አድርጐ በመጮህ ቤት የሚሠራ ቢሆን፤ አህያ በቀን በቀኑ ሁለት ቤት በሠራ ነበር!” ያሉት፡፡   

Published in ርዕሰ አንቀፅ

የመንግስት ፕሮጀክቶችና የሃብት ብክነት
መንግስት ቢዝነስ ውስጥ ገብቶ ሲያቦካና ኢኮኖሚው ውስጥ ድርሻው እያበጠ ሲመጣ፤ የዚያኑ ያህል የሃብት ብክነትና ቀውስ መፈጠሩ አይቀርም። ድሃ አገራት ውስጥ የሚፈጠረውን ብክነት ለመቁጠር መሞከር አስቸጋሪ ነው። ከብልፅግና ርቀው በድህነት የሚሰቃዩት ለምን ሆነና? ብዙ ሃብት ስለሚባክን ነው። መንግስት በገነነባቸው ድሃ አገራት ይቅርና፣ በአሜሪካና በአውሮፓ ውስጥም የመንግስት ብክነት ቀላል አይደለም። አንዳንድ ምሳሌዎችን ልጥቀስ-  ከአገራችን የመንግስት ብክነት ጋር እያያዝኩ፡፡ ቀለል ባሉት ብክነቶች እንጀምር፡፡
ጣሊያን እና ኢትዮጵያ
የጣሊያን መንግስት ከተመሳሳይ የአውሮፓ አገራት የሚለይበት ነገር ቢኖር፤ በመኪና ግዢ የሚስተካከለው አለመኖሩ ነው። ተመሳሳይ የሕዝብ ብዛትና የኢኮኖሚ ደረጃ ካላቸው አገራት ጋር ሲነፃፀር፤ የጣሊያን መንግስት በ10 እጥፍ የሚበልጡ መኪኖች እንዳሉት የዘገበው ዘ ኢኮኖሚስት፤ የመኪኖቹ ቁጥር 630ሺ ገደማ እንደሆነ ገልጿል። ከ10 ቢ. ዶላር በላይ ገንዘብ የባከነውና መኪኖች በገፍ የተገዙት በቂ ገንዘብ ስላለ አይደለም። ግን፤ መንግስት ገንዘብ መበደር ይችላል። የጣሊያን መንግስት እዳ፤ ከአመት አመት ሲከማች፣ አሁን 2.8 ትሪሊዮን ዶላር ደርሷል (2800 ቢሊዮን ዶላር!)። የመንግስትን የገንዘብ ብክነት እቀንሳለሁ በማለት ቃል የገቡት አዲሱ የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ለመነሻ ያህል 1500 የመንግስት የቅንጦት መኪኖችን ለመሸጥ ወስነዋል።
የኢትዮጵያ የሃብት ብክነት በጣም በጣም ይለያል። የተገዙ መኪኖች አገልግሎት ሳይሰጡ ይበላሻሉ፤ ሳይጠገኑ ይቆማሉ፡፡ ከትልልቅ የመንግስት ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው የውሃ ስራዎች ድርጅትን ማየት ይቻላል፡፡ ከአገልግሎት ውጭ የሆኑትን ሳይቆጠሩ 900 ገደማ ትልልቅ የኮንስትራክሽን መኪኖችና ማሽኖች አሉት፡፡ ነገር ግን ግማሾቹ ያለ አገልግሎት ቆመዋል፡፡
አብዛኞቹ ግማሽ አመት ገደማ ጋራዥ ውስጥ የተቀመጡ ናቸው፡፡ እናም የተለያዩ የግንባታ መኪኖችን ይከራያል፡፡ በአመት ለኪራይ ምን ያህል እንደሚያወጣ ታውቃላችሁ? አምና የድርጅቱ ጠቅላላ በጀት 1.8 ቢሊዮን ገደማ ነበር፡፡ ከዚህ ውስጥ አምና ወደ 700 ሚሊዮን ብር የወጣው ለተሽከርካሪዎች ኪራይ ነው፡፡ በእያንዳንዷ ቀን 1.9 ሚ. ብር መሆኑ ነው፡፡
በየቀኑ አንድ ገልባጭ መኪና ለመግዛት የሚያስከፍል ገንዘብ ለኪራይ ይከፍላል፡፡ በመንግስት አማካኝነት ከቻይና ተገዝተው የመጡ በመቶ የሚቆጠሩ “ሃይገር ባሶች” ንም መመልከት ይቻላል፡፡ ብዙዎቹ  በሁለት አመት እድሜ ከአገልግሎት ውጭ ሆነዋል፡፡ በድሃ አገር አቅም የሃብት ብክነቱ ከአውሮፓም ይብሳል፡፡   
ፈረንሳይ እና ተንዳሆ
በፈረንሳይ መንግስት ትዕዛዝ የተሰሩ ባቡሮች፣ ሰሞኑን መወዛገቢያና መሳለቂያ ሆነው ሰንብተዋል። የባቡሮቹ ስራ የተጀመረው ከሶስት አመት በፊት ቢሆንም፤ የጎን ስፋታቸው ከብዙዎቹ የባቡር ፌርማታዎች እንደሚበልጥ የተወራው ሰሞኑን ነው። ዎልስትሪት ጆርናል እንደዘገበው፤ በአገሪቱ ውስጥ ካሉት ከስምንት ሺ በላይ ፌርማታዎች መካከል፣ 1300 ያህሉ አዳዲሶቹን ባቡሮች ማሳለፍ አይችሉም። ሚኒስትሮችና የፓርላማ ፖለቲከኞች፣ የባቡር ድርጅት ባለስልጣናትና ቢሮክራቶች፣ አንዱ በሌላው ላይ ጣት እየቀሰሩ ቢወዛገቡም፣ መሳለቂያ ከመሆን አላመለጡም። ባቡሮቹን ደፍጥጦ ማሳነስ አይቻል ነገር! ፌርማታዎቹን ከጎንና ከጎን እየሸራረፉ ትንሽ ሰፋ ለማድረግ፣ ወደ 70 ሚሊዮን ዶላር ይመደባል ተብሏል - 1.4 ቢሊዮን ብር ገደማ መሆኑ ነው።
በኤልፓ የተገዙ መአት ትራንስፎርመሮች፣ ምን ሆነው እንደተገኙ ታውቁ ይሆናል፡፡ በጣም ያረጁና በየእለቱ የሚበላሹ የሃብት ብክነት ሆነው አረፉት፡፡ በየከተማው የቄራ ድርጅት እንሰራለን ተብሎ ሲሞከርስ ምን ተፈጠረ? የቄራው የጣሪያ ከፍታ፣ ለከብት እርድ እንደማይበቃ የተረጋገጠው ግንባታው ከተጠናቀቀ በኋላ ነው፡፡
የአገሪቱን የስኳር ምርት ከሁለት እጥፍ በላይ ያሳድጋል ተብሎ ከ10 አመት በፊት የተጀመረውን የተንዳሆ እቅድ ብንተወው ይሻላል፡፡ ቢሊዮን ብሮች የፈሰሰበት ፕሮጀክት ምን ያህሉ ለብክነት እንደተዳረገ አስቡት፡፡
አንድ ምሳሌ ብቻ ልጥቀስላችሁ፡፡ ለብዙ አመታት ከተጓተተ በኋላ ለስኳር ፋብሪካው የሚውል የሸንኮራ አገዳ በ5ሺ ሄክታር  መሬት ላይ ተተከለ፡፡ ፋብሪካው ግን ገና ነው፡፡ ምንም ማድረግ አልተቻለም፡፡ ሸንኮራው ባከነ - የ100ሚ ብር ብክነት፡፡
እንግሊዝ፡
የአገሪቱ አቃቤ ሕጎች፣ የወረቀት መዛግብት ከሚሸከሙ፣ በዘመኑ ቴክኖሎጂ እንዲጠቀሙ ተብሎ ነው 4600  ታብሌቶች (ጠፍጣፋ ሚኒኮምፒዩሮች) የተገዙት። ፍርድ ቤት ውስጥ ክርክር ሲያካሂዱም ሆነ ምስክሮችን ሲያፋጥጡ፣ ወረቀቶችንና ፋይሎችን መያዝ አያስፈልጋቸውም - ታብሌት ተሰጥቷቸዋል። አቃቤ ህጎቹ “ጥሩ ሃሳብ ነበር፤ ግን በታብሌቶቹ ክብደት እጃችን ዛለ” የሚል ቅሬታ ማሰማታቸውን የዘገበው ዋየርድ መፅሄት፤ የታብሌቶቹ ክብደት ወደ 2 ኪሎ ግራም ገደማ መሆኑን ገልጿል። እንደ ላባ የቀለሉ ታብሌቶችን ትቶ፣ እንደ ብረት የከበዱ ታብሌቶችን የገዛው ማን ይሆን? ያው የመንግስት ቢሮክራት ነዋ። እና ምን ተሻለ? የታብሌት ማስቀመጫ አትሮንስ በብዛት ለመግዛት ተወሰነ። ይሄ ትንሹ ብክነት ነው።
የእንግሊዝን የጤና ኢንሹራንስና አገልግሎት፣ በዘመናዊ የኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ለማሻሻል አዲስ ፕሮጀክት የተጀመረው በ2007 ነው። ከዚያ ወዲህ ለፕሮጀክቱ ከ15 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ፈስሷል። ውጤቱስ? የጤና ኢንሹራንስና አገልግሎት ትርምስምሱ ወጣ። ለማስተካከል እንዳይሞከር ደግሞ፤ ቴክኖሎጂው ጊዜው ያለፈበት ሆኖ ተገኘ። እናም፤ ሙሉ ለሙሉ በአዲስ ፕሮጀክት ሊለወጥ ይገባል ተብሏል። 15 ቢ. ዶላር ቀለጠች (300 ቢሊዮን ብር?)
ስኩል ኔት፣ ወረዳ ኔት፣ የዩኒቨርስቲዎች ቪዲዮ ኮንፈረንሲንግ ማዕከላት እየተባለ ስንት ቢሊዮን ብር እንደወጣ ይታወቃል። አንዳንዶቹ ከአስር አመት በላይ አስቆጥረዋል፤ አንዳንዶቹ ደግሞ አምስት አመት። እነዚህ ፕሮጀክቶች ምን አገልግሎት እየሰጡ ይሆን? ስኩል ኔት እና ወረዳ ኔት ለምን አገልግሎት ሊውሉ እንደሚችሉ እየታሰበበት ነው። የዩኒቨርስቲ ቪዲዮ ኮንፈረንሲንግ ማዕከላት፣ በወር አንዴ ለዚያውም ለጥቂት ደቂቃዎች ነው አገልግሎት የሚሰጡት። አንዳንዶቹማ ፣ በአመት አንዴ ከተከፈቱም ድንቅ ነው።
አሜሪካ እና ጀርመን ከአገራችን ጋር
የአሜሪካ መንግስት፣ አገልግሎት የማይሰጡ 50ሺ ቤቶች እንዳሉት የገለፀው ሄሪቴጅ ፋውንዴሽን፣ ለእነዚህ ቤቶች እድሳት በየአመቱ 25 ቢሊዮን ዶላር በጀት ይመደባል ብሏል። (በኢትዮጵያ አቅም፣ ስንት ሺ ቤቶች ናቸው፣ ሳይከራዩ ወይም ለሽያጭ ሳይቀርቡ ለአምስት አመታት ሲበላሹ የቆዩት?)
ለስልጠና፣ ለምግብ ዋስትና፣ ለማቋቋሚያ... ለምናምን እየተባለ በየአመቱ 125 ቢሊዮን ዶላር ገደማ በጀት ይመደባል - በአሜሪካ። አብዛኛው በጀት በከንቱ እንደሚባክን የገለፁት ጥናት እንዲያካሂዱ የተመደቡ የመንግስት ኦዲተሮች ናቸው። ወደ ሩብ ያህል የሚጠጋው በጀት ግን ሙሉ ለሙሉ ያለ አንዳች ውጤት የሚባክን ነው ብለዋል ኦዲተሮቹ - ወደ 30 ቢ. ዶላር በየአመቱ።
በአገራችንም እንዲሁ፣ ለምግብ ዋስትናና ለስልጠና፣ ለጥቃቅንና ለአነስተኛ ተቋማት፣ ለብድርና ለገበያ ትስስር በሚሉ እልፍ ሰበቦች ብዙ ብር ይባክናል፡፡
በየአመቱ ለግብርና ዘርፍ ከሚመደበው የብዙ ቢሊዮን ብር በጀት ውስጥ ገሚሱ፣ “የምግብ ዋስትና” ተብሎ ለሚታወቀው የድጐማና የእርዳታ ፕሮጀክት የሚውል ነው፡፡ 7.5 ሚሊዮን ያህል የገጠር ተረጂዎችንና ተደጓሚዎችን በመደገፍ ራሳቸውን እንዲችሉ አደርጋለሁ የሚለው መንግስት፤ በዚህ አመት ቁጥራቸውን ወደ 2 ሚሊዮን ዝቅ ለማድረግ አቅዶ ነበር - የዛሬ አራት አመት። ነገር ግን የተረጂዎቹና የተደጓሚዎቹ ቁጥር አሁንም ወደ 7 ሚሊዮን ገደማ ነው፡፡
ከእነዚህ በተጨማሪ የውጭ እርዳታ የሚቀበሉ 6.5 ሚሊዮን ሰዎች መኖራቸውን አትዘንጉ፡፡ በድምር 13 ሚሊዮን ተረጂ ማለት ነው፡፡ ጥቃቅንና አነስተኛ የምርት ተቋማትን በስልጠናና በብድር በመደገፍ በየአመቱ ከ15 በመቶ በላይ እንዲያድጉ የወጣው እቅድስ? በአንድ በኩል እቅዱ ሙሉ ለሙሉ…ከዚያም በላይ ተሳክቷል። ከታቀደው በላይ ለብዙ ወጣቶችና ተቋማት ስልጠና ተሰጥቷል - ብዙ ገንዘብ ተመድቦላቸው፡፡ በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ብድርም ተከፋፍሏል፡፡ ተሳክቷል፡፡ በሌላ በኩል ግን እቅዱ በጭራሽ አልተሳካም፡፡ እንዲያውም ከሌሎቹ የኢኮኖሚ ዘርፎች ጋር ሲነፃፀር አነስተኛና ጥቃቅን አምራች ተቋማት አመታዊ እድገታቸው፤ ባለፉት ሦስት አመታት እየቀነሰ አምና ወደ 3 በመቶ ወርዷል፡፡ በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ሃብት በከንቱ ባከነ አትሉም?




አባል ለመሆን፤ በቴሌኮም፣ በባንክና በኤሌክትሪክ ሃይል ኢንዱስትሪው የመንግስትን ድርሻና ቁጥጥር መቀነስ ግዴታ ነው

የኢትዮጵያ መንግስት በቴሌኮምና በባንክ ዘርፎች ላይ ያለውን ከፍተኛ ድርሻና ቁጥጥር በማቆም ዘርፎቹን ለአገር ውስጥና ለውጭ ኢንቨስትመንት እንዲከፍት የሚገደድ ከሆነ በመጪው አመት የአለም የንግድ ድርጅት አባል የመሆን እቅዱን እንደሚያራዝም የንግድ ሚኒስትር አቶ ከበደ ጫኔ ተናገሩ፡፡
ሚኒስትሩ ባለፈው ማክሰኞ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እንደተናገሩት፣ የአለም የንግድ ድርጅት አባል አገራት የኢትዮጵያ መንግስት የቴሌኮምና የባንክ አገልግሎት  ለአለማቀፍ ውድድር ክፍት የሚያደርግበትን ጊዜ በተመለከተ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች እያቀረቡ ነው፡፡
“የአገልግሎት ዘርፉን በተመለከተ በርካታ ጥያቄዎች እየተነሱ ይገኛሉ፡፡ የቴሌኮም፣ የባንክ እና የኤሌክትሪክ ሃይል ኢንዱስትሪዎችን ለግል ባለሃብቶች ክፍት የምናደርግበትን ጊዜ በግልጽ እንድናሳውቅ በተደጋጋሚ እንጠየቃለን” ያሉት ሚኒስትሩ፤ “የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን ከማጠናቀቃች በፊት፣ የህግ ማሻሻያዎችን በማድረግ የአገልግሎት ዘርፉን ለአገር ውስጥና ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት እንድናደርግ ጫና እየተደረገብን ይገኛል” ብለዋል፡፡
መንግስት ጉዳዩን በጥንቃቄ እንደሚይዘው ሚኒስትሩ ጠቅሰው፣ ከአለም የንግድ ድርጅት አባልነት ጋር በተያያዘ አስገዳጅ ቅድመ ሁኔታዎች የሚቀርቡ ከሆነ፣ አገሪቱ በ2015 አባል ለመሆን የያዘችውን ዕቅድ ልታራዝም ትችላለች ብለዋል፡፡
ከሁለት አመታት በፊት የጸደቀው የአለም የንግድ ድርጅት አዲስ ህግ፣ የእድገት ደረጃቸው እጅግ አነስተኛ የሆኑ የአለም አገራት የድርጅቱ አባል ለመሆን የሚችሉበትን መስፈርት በመጠኑ ቀለል እንዳደረገ የዘገበው ሮይተርስ፤ ድሃ አገራት የተለያዩ ዘርፎችን ቀስ በቀስ ወደ ግል ኢንቨስትመንት እንዲያዘዋውሩና ደረጃ በደረጃ ለአለማቀፍ ውድድር ክፍት እንዲያደርጉ የሚፈቅድ መሆኑን አስታውሷል፡፡
“የትኞቹ የአገሪቱ ህጎች ከአለም የንግድ ድርጅት ጋር እንደሚጣጣሙና፣ የትኞቹ እንደሚጣረሱ እየገመገምን ነው” ያሉት አቶ ከበደ፤ “እ.ኤ.አ በ2015 የንግድ ድርጅቱ አባል ለመሆን የያዝነው ዕቅድ ሊራዘም ይችላል” ብለዋል፡፡
አሁን ባለበት ሁኔታ አገሪቱን የአለም የንግድ ድርጅት አባል ለማድረግ ኢኮኖሚው አነስተኛ እንደሆነና የበለጠ ማደግ እንደሚገባው የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ የምትገኘው ቻይና፣ የአለም የንግድ ድርጅትን አባል  ለመሆን በርካታ አመታት ወስዶባታል ብለዋል፡፡
በፍጥነት በማደግ ላይ የሚገኘው የአገሪቱ ገበያ በተለይ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የውጭ አገራት ባለሃብቶችን መሳብ በመቻሉ፣ በርካታ የስዊድን፣ የቻይና እና የቱርክ ባለሃብቶች በዘርፉ ሰፊ ስራ እያከናወኑ እንደሚገኙ የጠቆመው የሮይተርስ ዘገባ፤ የአገሪቱ ህጎች የቴሌኮም እና የባንክ አገልግሎት በመሳሰሉ ፖለቲካዊ ችግር ሊያስከትሉ ይችላሉ ተብለው በሚታሰቡ ዘርፎች የውጭ ኢንቨስትመንትን ያግዳሉ ብሏል፡፡

Published in ዜና

ወ/ሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ በታዋቂው ሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ፤ በታፈነ ማህበረሰብ ውስጥ የዳኝነት ነጻነት ምን እንደሚመስል /independence of the judiciary in closed societies/  የሁለት ዓመት ጥናት በመከታተል ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አገኙ፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክ በተቃዋሚ ፓርቲ አባልነትም ሆነ በግል ተወዳዳሪነት ሴት ፖለቲከኞች ወደ አደባባይ በማይወጡበት ወቅት በግል ተወዳዳሪነት የተሳተፉት ወ/ሪት ብርቱካን፤ በ1997ዓ.ም. በዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እና በፕ/ር መስፍን ወልደማርያም በተመሰረተው ቀስተደመና ፓርቲ አባል የሆኑት በ1997 ዓ.ም ነው፡፡
ቀስተደመና ቅንጅትን ከፈጠሩት ፓርቲዎች መካከል አንዱ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን ከምርጫው በኋላ ነው ወ/ሪት ብርቱካን የቅንጅት ሊቀመንበር እንዲሆኑ የተመደቡት፡፡ በ2001ዓ.ም. የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ መስራች በመሆን ሰርተዋል፡፡
ከምርጫ 97 ቀውስ ጋር በተያያዘ ሁለቴ ለእስር የተዳረጉት ወ/ሪት ብርቱካን፤ በሊቀመንበርነት ይመሩት ከነበረው አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ የተሰናበቱ ሲሆን፤ ስንብታቸውን ተከትሎ በፖለቲካው ዓለም ይቀጥሉ እንደሆነ የተለያዩ ወገኖች ጥያቄ ሲያነሱ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡ ወ/ሪት ብርቱካን ሚዲቅሳ የአንዲት ሴት ልጅ እናት ናቸው፡፡

Published in ዜና

    የአዲስ አበባ የቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ የሚያስገነባቸው የ40/60 ቤቶች አይነትና የተመዝጋቢው ፍላጐት እንደማይጣጣም መረጃዎች ያመለክቱ ሲሆን፤ የኢንተርፕራይዙ እቅድ በተለይ ባለ 2 እና ባለ 3 መኝታ ቤት የሚፈልጉ ተመዝጋቢዎችን ማስተናገድ አይችልም ተባለ።  
ቀደም ብሎ በተዘጋጀው እቅድ ላይ ባለ አንድ፣ ባለሁለት እና ባለ ሶስት መኝታ ቤቶችን ጨምሮ ንግድ ቤቶች የተካተቱ ሲሆን ባለ 1 መኝታ ቤት ፈልገው የተመዘገቡት ከተገመተው በታች ሆኗል። ባለ ሁለት እና ባለ ሶስት መኝታ ቤት ፈልገው የተመዘገቡት ደግሞ፤ ከተገመተው ከእጥፍ በላይ ይበልጣል፡፡ ለንግድ ቤቶች ግን አንድም ተመዝጋቢ አልተገኘም፡፡
በአዲስ አበባ አስተዳደር እቅዱ ላይ ከአጠቃላይ ተመዝጋቢ መካከል 35 በመቶ የሚሆነው ባለ አንድ መኝታ ቤቶችን ምርጫው ያደርጋል ተብሎ የተጠበቀ አስር በመቶ ቢሆንም (ወደ 17ሺ ገደማ) ቤት ፈላጊዎች ብቻ ናቸው የተመዘገቡት፡፡ ከአጠቃላይ ተመዝጋቢው 25 በመቶው ደግሞ በባለ ሁለት መኝታ ቤት ይመዘገባል ተብሎ ቢጠበቅም ከተገመተው በላይ 46 በመቶ (76ሺ ገደማ እንደተመዘገበ ታውቋል፡፡ ለባለ ሶስት መኝታ ቤትም እንዲሁ 20 በመቶ የተጠበቀ ሲሆን የተመዘገበው ግን 44 በመቶ (73ሺ ገደማ) ናቸው፡፡  
ፕሮጀክቱን የሚመሩ ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ የተመዝጋቢውን ቁጥር ከቤቶቹ አይነት ጋር ለማመጣጠን በሚል፣ ቀደም ሲል የወጣው የቤቶች ዲዛይን እንዲለወጥ ተደርጓል፡፡ ቀደም ሲል ባለ 12፣ ባለ 9 እና ባለ 7 ፎቅ ቤቶች ይሰራሉ ተብሎ የታቀደ ቢሆንምበአሁን ሰአት ባለ 18 እና 24 ፎቅ አዳዲስ ዲዛይን መዘጋጀቱን ባለሙያዎቹ ገልፀዋል፡፡
በሌላ በኩል በሰንጋተራ ሳይት በግንባታ ላይ ያሉት ቤቶች ቀደም ሲል ቤት ፈላጊዎች ከተመዘገቡበት እና በስትራቴጂክ እቅዱ ከተቀመጠው የስፋት መጠን የተለዩ መሆናቸውንም ባለሙያዎች ጠቁመዋል፡፡ በባለ 12 እና ባለ 9 ፎቅ ቤቶች ግንባታ ላይ ቀደም ሲል ቤት ፈላጊዎች ባለ አንድ መኝታ ቤት 55 ሜትር ስኩየር ስፋት ይኖረዋል ተብለው የተመዘገቡ ቢሆንም በዲዛይን ላይ የተቀመጠው የቤቶቹ ስፋት 96.72 ሜትር ስኩየር ሲሆን በምርመራው ሂደትም በመሬት ላይ የሰፈረው 85.4 ሜትር ስኩየር ሆኖ መገኘቱን ባለሙያዎች አስረድተዋል፡፡ በተመሳሳይ ባለ 2 መኝታ ቤት ቤት ፈላጊዎች ሲመዘገቡ 75 ሜትር ስኩየር ስፋት ይኖረዋል ተብሎ የነበረ ቢሆንም ዲዛይኑ ላይ 115.81 ሜትር ስኩየር ሆኖ በተግባር የተሰራው ደግሞ 116.2 ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ባለ ሶስት መኝታ ቤትን በተመለከተም 100 ሜትር ስኩየር ይኖረዋል የተባለው ቤት በዲዛይኑ ላይ 128 ሜትር ስኩየር ሆኖ መሬት ላይ ተሰራው በ129.5 ሜትር ስኩየር ሆኖ መገኘቱን ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡ በሌሎች ቤቶች ላይም ተመዝጋቢው በሚያውቀው ስፋት፣ በዲዛይኑ ላይ ባለው እና መሬት ላይ በወረደው ስፋት መጠን መካከል ልዩነቶች መኖራቸውን ምንጮቻችን ጨምረው ጠቁመዋል፡፡ ይህ መሆኑም የግንባታ ወጪው ስለሚጨምር ምናልባት የቤቱን የማጠናቀቂያ ስራዎች ወጪ ለባለ እጣዎች ሊተው ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ባለሙያዎች ገልፀዋል፡፡
ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት በአንድ ህንፃ ላይ በአማካይ ወደ 1ሺህ ሰው የሚጠጋ ይኖራል ተብሎ የሚገመት ሲሆን እነዚህን ሁሉ ያመላልሳል ተብሎ ለታሰበው ሊፍት የተተወው ክፍተት ቢበዛ 8 ሰዎችን ብቻ በአንድ ጊዜ ማመላለስ ለሚያስችል ሊፍት መሆኑን በማመልከት ህንፃው የነዋሪውን ምቾት የማሟላቱ ጉዳይ አጠራጣሪ ነው ብለዋል፡፡ ህንፃዎቹ ከሚይዙት የነዋሪ ብዛት እንዲሁም የነዋሪውን የተለያዩ ቁሳቁሶች ከማጓጓዝ አንፃር በሌሎች ሃገሮች በታየው ተሞክሮ መሰረት በአንድ ጊዜ እስከ 20 ሰው ማጓጓዝ የሚችሉ ሊፍቶች መገጠም ይገባቸው ነበር ሲሉ ባለሙያዎቹ ይመክራሉ፡፡
በአጠቃላይ ለ40/60 የቤት ፕሮግራም በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ 164 ሺህ 779 ቤት ፈላጊዎች የተመዘገቡ ሲሆኑ የመጀመሪያዎቹ እድለኞች በቀጣይ ዓመት ቤታቸውን እንደሚረከቡ ተናግሯል፡፡
ከጥር 2005 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን የ13ሺህ 881 ቤቶች ግንባታ እየተከናወነ ሲሆን በቀጣዩ ዓመት የ15ሺህ ቤቶች ግንባታ ይጀመራል ተብሏል፡፡  

Published in ዜና

በአዲስ አበባ ገርጂ አካባቢ በሚገኘው የኢትዮ ፓረንትስ ት/ቤት የ11ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ታዳጊ፤ የት/ቤቱን ዩኒት ሊደር አቶ ወንደሰን ተሾመን ሦስት ቦታ በጩቤ በመውጋት ተጠርጥራ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ስትውል፣ ተጐጂው በኮርያ ሆስፒታል በህክምና ላይ እንደሚገኙ ምንጮች ጠቆሙ፡፡ ለት/ቤቱ አዲስ ነች የተባለችው ተማሪ ትናንት ከጠዋቱ 5፡30 ላይ ወደ ዩኒት ሊደሩ ቢሮ ለቤተሰብ ስልክ ደውልልኝ በማለት ከገባች በኋላ አደጋውን እንዳደረሰች ታውቋል፡፡ ተማሪዋ አስተማሪውን ለምን በጩቤ እንደወጋች እስካሁን አልታወቀም።
አደጋው የደረሰባቸው የት/ቤቱ ዩኒት ሊደር አቶ ወንድወሰን ተሾመ፤ ከመምህርነታቸው በተጨማሪ፣ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ እንደሆኑ ታውቋል።

Published in ዜና

በሐረር ከተማ “ማሳደግ አልችልም” በሚል ሰበብ የወለደችውን ህፃን በፌስታል አድርጋ መፀዳጃ ቤት ጉድጓድ ውስጥ የከተተች እናት በቁጥጥር ስር የዋለች ሲሆን ህፃኑ ከ6 ሰዓት በኋላ ከጉድጓዲ ወጥቶ ህይወቱ ተርፏል፡፡
በሐረሪ ክልል በቀበሌ 19 ልዩ ስሙ አማሪሳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ የሆነችው የ20 ዓመቷ ወጣት፤ ባለፈው ሐሙስ ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ላይ የተገላገለችውን ህፃን በፌስታል አድርጋ መፀዳጃ ቤት ጉድጓድ ውስጥ እንደከተተችው የክልሉ ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ኮማንደር ጣሰው ቻለው ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ላይ ወደ ሽንት ቤት ያመራ ጎረቤት የህፃኑን ለቅሶ ሰምቶ ለፖሊስ መጠቆሙንና ህፃኑ በመፀዳጃ ቤቱ ጉድጓድ ውስጥ ተንሳፎ በህይወት መገኘቱን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ገልፀዋል፡፡
በቀን ሥራ የምትተዳደረው እናት ቤቷ ውስጥ ተኝታ መገኘቷን የገለፀው ፖሊስ፤ ህፃኑን መፀዳጃ ቤት ውስጥ የከተተችው የማሳደግ አቅም ስለሌላት እንደሆነ በመናገር ድርጊቱን መፈፀሟን አምናለች ብሏል፡፡ህፃኑ በሐረር ከተማ በሚገኘው የህይወት ፋና ሆስፒታል በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኝ ፖሊስ ጠቁሞ፤ እናትየው ምርመራ እየተደረገባት እንደሆነ ገልጿል፡፡  

Published in ዜና

ካቻምናም ታፍኛለሁ፣ ዘንድሮ ግን በህግ እጠይቃለሁ ብሏል

ተቀማጭነቱን በሳዑዲ አረቢያ ያደረገውና በርካታ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚያሰራጨው የአረብ ሳተላይት ኮሙኒኬሽን ተቋም (አረብሳት) ካለፈው ሳምንት ጀምሮ እየተፈጸመበት ያለው ዓለማቀፍ የሳተላይት ሞገድ አፈና (Jamming) ምንጩ ከኢትዮጵያ መሆኑን እንዳረጋገጠ ገለጸ፡፡
ሳትኒውስ የተባለው የአገሪቱ የዜና ምንጭ ከትናንት በስቲያ እንደዘገበው፣ አረብሳት በሚያስተላልፋቸው በርካታ የቴሌቪዝን ጣቢያዎቹ ላይ መታየት የጀመረውን የስርጭት መስተጓጎል መነሻ ለማወቅ ባደረገው በረቂቅ ቴክኖሎጂ የታገዘ ጥናት፣ ከኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የሚነሳና ሆን ተብሎ የሚፈጸም የሳተላይት ሞገድ አፈና (Jamming) እየተደረገበት መሆኑን ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡ ይህን መሰሉ ህገወጥ ድርጊት መፈፀሙ መሆኑ እጅግ እንዳሳዘነው ያስታወቀው አረብሳት፤ ከኢትዮጵያም ሆነ ከኤርትራ የሚተላለፍ ምንም አይነት ስርጭት ሳይኖረው፣ የሳተላይት ሞገድ አፈና መደረጉ እንቆቅልሽ እንደሆነበት ገልጿል፡፡
የሳተላይት ሞገድ አፈናው፣ ምናልባትም ከሁለቱ አገራት የአንዱ ተቀናቃኝ የሆኑና ከአረብሳት ሳተላይቶች አቅራቢያ በሚገኙ ሳተላይቶች አማካይነት የሚሰራጩ የቴሌቪዝን ጣቢያዎችን ለማፈን የታለመ ሊሆን እንደሚችል ያለውን ግምትም ሰጥቷል፡፡
እየተፈጸመበት ያለውን ህገወጥ ተግባር ለመመከት በብሄራዊና በአለማቀፍ ደረጃ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የገለጸው አረብሳት፣ ጉዳዩን ለዓለማቀፉ የቴሌኮምኒኬሽን ህብረት እና ለአረብ ሊግ ማሳወቁንም ጠቅሷል፡፡አረብሳት ጉዳዩን በቀጣይ ከመረመረ በኋላ፣ ከአለማቀፍ የህግ  ተቋማትና የአገሪቱ የህግ አካላት ጋር በመቀናጀት ወደ ህግ እንደሚያመራና እየተቃጣበት ባለው የሳተላይት ሞገድ አፈና ለደረሰበትም ሆነ ለሚደርስበት ጉዳት ካሳ እንደሚጠይቅ  ማቀዱን ተናግሯል፡፡ከሁለት አመታት በፊት ከኢትዮጵያ ተመሳሳይ የሳተላይት ሞገድ አፈና እንደተፈጸመበትም አስታውሷል።

Published in ዜና

የተከሳሾች መቃወሚያ ውድቅ ሆኗል

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት 15ኛ ወ/ችሎት የሙስና ክስ የቀረበባቸውን የቀድሞ ገቢዎችና ጉምሩክ ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታንና በሶስት መዝገቦች የተከሰሱ ሌሎች ተከሳሾችን የክስ መቃወሚያና የአቃቤ ህግን ምላሽ መርምሮ በትናንትናው እለት ብይን ሰጠ፡፡ ፍ/ቤቱ አብዛኛውን የተከሳሾችን መቃወሚያ ውድቅ አድርጓል፡፡
ፍ/ቤቱ ብይኑን ከመስጠቱ በፊት ተከሳሾቹ ያመለከቱትን የክስ መቃወሚያና የአቃቤ ህግን ምላሽ አስታውሷል፡፡
በመዝገቡ 1ኛ ተጠሪ የሆኑት አቶ መላኩ በዚህ መዝገብ በቀረቡባቸው ክሶች፤ የቀረቡብኝ ክሶች በስነ ስርአት ህጉ አንቀፆች መሰረት የተሟሉ አይደሉም፣ ከባለስልጣናት ጋር በመመሳጠር ክስ አንስተሃል ለተባልኩት ኃላፊነት የለብኝም” የሚሉና ሌሎች መቃወሚያዎችን ያስታወሰው ችሎቱ፤ አቶ ገ/ዋህድ በበኩላቸው፤ “በተነሱና በተቋረጡ ክሶች ልጠየቅ አይገባም፤ ክሶችን እንዳነሣ አዋጁም ይፈቅድልኛል፤ ከተፈቀደልኝ ወሰን በላይ ህግ አልጣስኩም” ማለታቸውን ጠቁሟል፡፡
ሌሎች በመዝገቡ የተካተቱ ተከሳሾች “የቀረበው ክስና ማስረጃ ግልፅ አይደለም፣ በተሻረ የህግ አንቀፅ ተከሰናል፣ ኮሚሽኑ በማይመለከተው ስልጣንና በሌለው ውክልና ነው የከሰሰን፣ ክሱ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ነው” የሚሉና ሌሎች በርካታ መቃወሚያዎች እንዳቀረቡም ችሎቱ አስታውሷል፡፡
ለተከሳሾቹ መቃወሚያ ከአቃቤ ህግ ከተሰጡ ምላሾች መካከልም፤ ከማስረጃና ከክስ ጭብጥ ጋር ተያይዞ የቀረቡት መቃወሚያዎች በብይን ሳይሆን በክርክር ሂደት ነው መታየት ያለባቸው የሚለው ይገኝበታል፡፡
እነ አቶ መላኩ በእርግጥም ክስ የማንሳት ስልጣን በአዋጅ እንደተሰጣቸው የጠቀሰው አቃቤ ህግ፤ ነገር ግን ተከሳሾቹ ከተፈቀደላቸው የህግ ወሰን በላይ የተሰጣቸውን መብት ተጠቅመዋል ሲል ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ሁሉም ተከሳሾች ያቀረቡት የክስ መቃወሚያም ሙሉ ለሙሉ ውድቅ እንዲደረግለት አቃቤ ህግ የጠየቁ ሲሆን፡፡
የግራ ቀኙን መከራከሪያ ሲመረምር መቆየቱን ያስታወሰው ፍ/ቤቱም፤ በዚህ መዝገብ ላይ ክሱ መስፈርቱን አሟልቶ መቅረቡን እንዲሁም ገቢዎችና ጉምሩክ ለፀረ-ሙስና ኮሚሽን ውክልና መስጠት እንደሚችል በመግለፅ በመዝገቡ ከተጠቀሱት 93 ክሶች 90ዎቹ ባሉበት እንዲቀጥሉ ሶስቱ ተሻሽለው እንዲቀርቡ በይኗል፡፡
ፍ/ቤቱ ቀጣይ ሂደቱን ለማየት ሁሉንም መዝገቦች ለሰኔ 3 ቀን 2006 ዓ.ም ቀጥሯል፡፡

Published in ዜና

በዕንቁ መጽሔት ላይ ባለፈው መጋቢት ወር “እየተገነቡ ያሉ ሃውልቶች የማንና ለማንስ ናቸው?” በሚል ርዕስ ከወጣ ፅሁፍ ጋር በተገናኘ ከፖሊስ ጥሪ ደርሶት ወደ ማዕከላዊ ፖሊስ የሄደው የመጽሔቱ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ አልያስ ገብሩ፤ ከ3 ቀን እስር በኋላ ከትናንት በስቲያ  በ30ሺ ብር ዋስ ተለቀቀ፡፡
በመጽሔቱ ላይ የወጣው ጽሑፍ፤ ከሁለት ወር በፊት በጅማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ለግጭት ማነሳሳቱን የጠቆመው ፖሊስ፣ ግጭቱን ተከትሎ በሰውና በንብረት ላይ ለደረሰው ጉዳት መጽሔቱን  ተጠያቂ አድርጐታል፡፡
ዋና አዘጋጁ ሰኞ ከሰዓት በኋላ ማዕከላዊ ፖሊስ ቀርቦ የተለያዩ ጥያቄዎች ከቀረቡለት በኋላ፣ “ጀርባውን ማጥናት ያስፈልጋል” በሚል የዋስትና መብቱ ተከልክሎ፣ በእስር እንዲቆይ መደረጉን ተናግሯል፡፡ በነጋታው ማክሰኞ ፍ/ቤት ቀርቦ ለፖሊስ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ የጠየቀ ሲሆን ፍ/ቤቱ የሰባት ቀን ቀጠሮ ፈቅዷል፡፡ የዋስ መብቱን ተከልክሎ ለተጨማሪ ሁለት ቀን በእስር መቆየቱን የገለፀው የመፅሄቱ ዋና አዘጋጅ፤ ከትላንት በስቲያ በ30 ሺ ብር ዋስ መፈታቱን ለአዲስ አድማስ ጠቁሟል፡፡ ሐሙስ ዕለት ፖሊስ ጠርቶ እንዳነጋገረው ጠቅሶ፤ “ከአሁን በኋላ እንዲህ አታደርጉ፤ የሚከፋፍል ሳይሆን አንድነትን የሚያጠናክር ነገር ፃፉ” የሚል ምክር እንደሰጠውና ዋስ ጠርቶ መለቀቁን ተናግሯል - ዋና አዘጋጁ፡፡
ከፅሁፉ ጋር በተገናኘ ቀድሞ የተጠየቀውም ሆነ የደረሰው መረጃ አለመኖሩን የገለፀው ኤልያስ፤ የዋስ መብት ተከልክዬ መታሰሬ የፕሬስ ህጉን ይፃረራል ብሏል።
“ከፅሁፍ ጋር በተገናኘ ለሚመጣ ቅሬታ ዋና አዘጋጁ ለምርመራ ፖሊስ ጋ መቅረቡ የተለመደ ነው፤ ነገር ግን በእስር አይቆይም፤ በዋስ ተለቆ ጉዳዩን ውጪ ሆኖ ይከታተላል” ያለው ዋና አዘጋጁ፤ የዋስ መብት ተከልክዬ መታሰሬ አግባብ አይደለም ብሏል፡፡

Published in ዜና
Page 5 of 21