Saturday, 31 May 2014 14:07

ሲያጌጡ ይመላለጡ!

ባለረጃጅም ተረከዝ ጫማዎች
በርካታ ሴቶች ረጃጅም ተረከዝ (ሂል) ያላቸውን ጫማዎች ያደርጋሉ፡፡ እነዚህ ጫማዎች መደበኛውን የሰውነት ክብደት ስርጭት በማዛባትና በእግሮች ላይ ጫና በመፍጠር እግር ያሳብጣሉ፡፡ የእግር ጣቶች አጋማሽ ላይ ድድር እባጮች (Knobs) በመፍጠር የእግርን ውበት ያጠፋሉ፡፡ ሰውነት ቅርፅ መዛባትም ያጋልጣሉ እንዲፈጠርም ሰበብ ይሆናሉ፡፡

አስጨናቂ ቀበቶዎች
ሆድን ጥብቅ አድርገው የሚይዙና ቅርፅን አጉልተው የሚያወጡ ቀበቶዎች፣ በፋሽኑ ዓለም እጅግ የተለመዱ ቢሆኑም በጤና ላይ የሚያስከትሉት ችግር ግን በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ የወገብን ዙሪያ ጥብቅ አድርገው የሚይዙ ቀበቶዎች፣ የአተነፋፈስ ስርአት እንዲዛባ በማድረግ፣ በቂ መጠን ያለው ኦክሲጅን ወደ ሳንባችን እንዳይገባ የግዳሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የምግብ መላም ሂደት እንዲስተጓጎልና ምግብ በአንጀታችን ውስጥ በበቂ ሁኔታ እንዳይንሸራሸር ያደርጋሉ፡፡ ይህም በጨጓራችን ላይ መጨናነቅን በመፍጠር፣ የልብ ማቃጠል ስሜትን ያስከትላል፡፡ ጥብቅ አድርጎ የሚይዝ ቀበቶን ማድረጉ ግድ ከሆነብዎ፣ አለፍ አለፍ እያሉ ቀበቶዎን በማላላት፣ ሰውነትዎን ማዝናናት አስፈላጊ መሆኑን አይዘንጉ፡፡


የጡት መያዣ ጣጣ
በሚያምር የጡት መያዣ ተወጥረው፣ ጉች ጉች ያሉ ጡቶችን ማየት ለተመልካቹ አስደሳች  ቢሆንም ያለልክ የሚደረጉ የጡት መያዣዎች ለተጠቃሚዎቹ ጤንነት አደገኛ ነው፡፡ ፋሽን ተከታይ ሴቶች፤ የጡታቸውን መጠን በማሳነስና ጡታቸውን አጥብቀው በመያዝ ለእይታ ማራኪ የሆነ ቅርፅ የሚያወጡ ጡት መያዣዎችን በብዛት ይጠቀማሉ፡፡
አንዳንድ ሴቶች ዕድሜያቸው እየጨመረና የሰውነት ክብደታቸው እየገዘፈ ቢሄድም፣ ልጅ ቢወልዱም የሚጠቀሙባቸውን የጡት መያዣዎች ቁጥር ለመጨመርና ልካቸው የሆኑ የጡት መያዣዎችን ለማድረግ ፍላጐት የላቸውም፡፡ እነዚህ ያለ ልክ የሚደረጉ ጡት መያዣዎች ደግሞ ትክክለኛ የደም ዝውውርን በማዛባት፣ የጡት አካባቢ ህመሞችን ከመፍጠራቸውም በተጨማሪ በአከርካሪ ላይ ጫና በመፍጠርና፣ እጅግ አደገኛ የሆነ የጀርባ ህመም ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡


ፎርጅድ የፀሐይ መነፅሮች
ጥቋቁር የፀሐይ መነፅሮችን መጠቀም በዘመናችን ወጣቶች ዘንድ እጅግ የተለመደ ነው። ኃይለኛ የፀሐይ ብርሃንን ለመከላከል ይረዳሉ እየተባሉ ከየገበያው ላይ በስፋት እየተሸመቱ የሚደረጉ መነፅሮች ሁሉ የፀሃይ ብርሃንን ይከላከላሉ ብሎ ማመኑ ግን ሞኝነት ነው፡፡ ይልቁንም አንዳንድ ጥቋቁር መነፅሮች፣ ጨረሮችን ወደ አይናችን በመሳብ አይናችንን ለከፍተኛ ጉዳት እንደሚያጋልጡ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ እነዚህ መነፅሮች አይንን የሚጎዱ ዩቪ የተባሉ ጨረሮችን ወደ አይናችን በመሳብ፣ ለአይን መቅላትና ብርሃንን የመቋቋም አቅም ለማጣት ችግር ያጋልጡናል፡፡ ሬቲና የተባለው የአይናችን ክፍል ጉዳትና ካታራክትስ የተባለው የአይን በሽታም በዚሁ መነፅር ሳቢያ እንደሚከሰቱ የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ስለዚህም ለፀሐይ ጨረር መከላከያ የምንጠቀምባቸው መነፅሮች በባለሙያ ማረጋገጥ ይመከራል፡፡


ለጠቅላላ እውቀት
በአውሮፕላን በምንጓዝበት ጊዜ 6 በመቶ ያህል ለጭንቅላት ህመም እንጋለጣለን፡፡
ምድርን ለቀን ወደ ሰማይ ስንወጣ፣ ስበት ስለሚቀንስ ሲሆን ጭንቅላታችን ለአደጋ የመጋለጡ ዕድሉም እየጨመረ ይሄዳል፡፡
አንድ ሰው በቀን 70ሺ ሃሳቦችን የማሰብ አቅም አለው፡፡
የጭንቅላታችን 75 በመቶ ያህሉ ውሃ ነው።
ጭንቅላታችን ኦክስጅን ሳያገኝ በህይወት መቆየት የሚችለው ከ4-6 ደቂቃዎች ብቻ ሲሆን፤ የደም እጥረት ሲገጥመው ደግሞ ከ10 ደቂቃ በኋላ በህይወት አይቆይም፡፡
የጤናማ ሰው አንጎል በአማካይ 100 ቢሊዮን ነርቮች አሉት፡፡
ከአንጎል ወደ አንጎል የሚደረገው የነርቭ ምልልስ አማካይ ፍጥነት፣ በሰዓት 274 ኪ.ሜ ነው፡፡    

Published in ዋናው ጤና

የውጭ አገር ህክምና ማግኘት ከሚገባቸው ህሙማን መካከል የሚሳካላቸው ከ5 በመቶ በታች ናቸው

           የገጠመውን የደም ካንሰር በሽታ በአገር ውስጥ ህክምና ለማዳን ባለመቻሉ፣ ወደ ውጭ አገር ሄዶ መታከም እንደሚስፈልገው የሚገልፀው የህክምና ማስረጃ እስኪሰጠው ድረስ ህመሙ ተስፋ አስቆራጭ አልሆነበትም ነበር፡፡
የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሃኪሞች ቦርዱ ፈርሞ በሰጠው ማስረጃ ላይ ህክምናውን በሁለት ወራት ውስጥ ማግኘት ካልቻለ በህይወት የመቆየት እጣ ፈንታው አጠያያቂ እንደሆነ በግልፅ ሰፍሯል፡፡ ሁኔታው እጅግ አስደንጋጭ ነበር፡፡ በቀድሞ የኢትዮጵያ ቴሌኮምኒኬሽን በአሁኑ ኢትዮ-ቴሌኮም ውስጥ ለአራት አመታት ሲሰራ ቆይቶ ድርጅቱ ባደረገው የአሰራር ለውጥ ሳቢያ ከስራቸው ከተፈናቀሉት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞች መካከል አንዱ ነው፡፡ ከስራው ከተፈናቀለ ወዲህ ቤተሰቡን የሚያስተዳድረው በሙያው በግል እየተሯሯጠ በሚያገኛት የዕለት ገቢ ነው፡፡ ገቢው ባለቤቱንና ሁለት ህፃናት ልጆቹን እንዳቅሙ ለማስተዳደር አስችሎታል፡፡ አልፎ አልፎ የሚሰማው ከባድ የህመም ስሜት እንዲህ እንዳሁኑ ዛሬ አልጋ ላይ ሳያውለው በፊት ሥራውን ለማስተጓጎልና ከቤት ለማዋል ሲታገለው እንደምንም እያሸነፈው ወደ ሥራው ይሄድ ነበር፡፡ የህመም ስሜቱን ለማስታገስና ስቃዩን ለመቋቋም የተለያዩ ማስታገሻ መድሃኒቶችን ሲወስድ ቆይቷል፡፡ ቀስ በቀስ ህመሙ እየባሰበት ስቃዩ እረፍት እየነሳው ሲሄድ ወደ ሃኪም ቤት ለመሄድ ተገደደ፡፡ ህመሙ ከበድ ያለ በመሆኑ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሄዶ መታየት እንዳለበት በተነገረው መሰረትም ወደ ሆስፒታሉ ሄዶ ምርመራ አደረገ፡፡ የምርመራው ውጤትም በሽታው ሥር የሰደደና በአገር ውስጥ ህክምና ሊድን የማይችል የደም ካንሰር ህመም መሆኑ ተነገረው፡፡ በሁለት ወራት ውስጥ ህክምናውን ማግኘት ካልቻለ ህይወቱ አደጋ ላይ እንደሚወድቅም የሆስፒታሉ የህክምና ቦርድ አረጋገጠለት፡፡ ለዚህ ህክምና ከ120 ሺህ ዶላር በላይ ያስፈልገዋል ተባለ፡፡ ፋሲል ይህንን መርዶ ከሰማ ቀን ጀምሮ እንቅልፍ ይሉ ነገር በአይኑ እንዳልዞረ አጫውቶኛል፡፡ አሁን በቀን አምስት መቶ ብር እየከፈለ ለእርዳታ ማሰባሰቢያነት በሚጠቀምበት ሚኒባስ መኪና ውስጥ ተኝቶ ለሞት የቀሩትን ቀናት ይቆጥራል፡፡ ከመኪና ኪራይ፣ ከእርዳታ ጠያቂቁው ሰው ዕለታዊ ክፍያና ከልዩ ልዩ ወጪዎች የሚተርፈውን ጥቂት ገንዘብ ለመድሃኒቶች መግዣና ለዕለት ወጪው እንደሚያውለውና ወደ ውጭ አገር ሄዶ የመታከም ተስፋው እንደጨለመም ነግሮኛል፡፡ ወደ ውጭ አገር ሄዶ አለመታከሙ ከሚፈጥርበት ስጋት ይልቅ ለሞት የቀሩትን ቀናት መቁጠር ይበልጥ እንደሚያስጨንቀውም አልደበቀኝም፡፡
የፋሲልን አይነት እጣ ፈንታ ገጥሟቸው በመኖርና ባለመኖር፣… በህይወትና በሞት፣ ለመኖር በመጓጓትና ለሞት በሚደረግ ጉዞ ሰቀቀን ውስጥ ሆነው ለወገኖቻቸው የድረሱልን ጥያቄ የሚያስተጋቡ ወገኖች እየተበራከቱ ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች ለውጭ አገር ህክምና ገንዘብ ለማግኘትና ለከፋ ህመምና ስቃይ ከዳረጋቸው ህመም ለመገላገል እጅግ በመጓጓት፣ የወገኖቻቸውን እርዳታና ድጋፍ ፍለጋ ደጅ መጥናታቸው በከተማችን የተለመደ ጉዳይ ሆኗል፡፡
በህይወት በመኖርና ባለመኖር ከባድ ፈተና ውስጥ ወድቀው ከህመም ስቃያቸው ጋር እየታገሉ ለመኖር በመጓጓት፣ በሰቀቀን ውስጥ ሆነው ለወገኖቻቸው የድረሱልኝ ጥሪያቸውን ከሚያስተጋቡት እጅግ በርካታ እርዳታ ጠያቂዎች መካከል ያሰቡት ተሳክቶላቸው፣ ለህክምናቸው የሚያስፈልጋቸውን ወጪ አሟልተው ከህመማቸው የሚፈወሱና ከስቃያቸው እፎይታን የሚያገኙት እጅግ ጥቂቶች ብቻ ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ እርዳታ ጠያቂ ህሙማን፤ በገንዘብ ማጣት ምክንያት በጊዜ መታከም ያልቻለ ህመማቸው ሥቃያቸውን እያበረታ፣ ወደ ሞት የሚያደርጉትን ጉዞ ሲያፋጥነው ማየቱ አዲስ ነገር አይደለም፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ጥናት ያደረጉት ዶ/ር ፍቃዱ ተስፋዬ እንደሚናገሩት፤ በአገር ውስጥ ህክምና መዳን በማይችሉ የጤና ችግሮች ተይዘው የውጭ ህክምና ማግኘት ካለባቸው ህሙማን መካከል ህክምናውን አግኝተው ለፈውስ የሚበቁት ከ5 በመቶ በታች ናቸው፡፡ ባለሙያው እንደሚገልፁት፤ አብዛኛዎቹ ህሙማን ለህክምና የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ ማሟላት ባለመቻላቸው ምክንያት ለከፋ ሥቃይና ሞት ይዳረጋሉ፡፡ በውጭ አገር ለሚደረገው ህክምና የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ፣ ገንዘቡን በእርዳታና መሰል ሁኔታዎች አሟልቶ ህክምናውን ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን የሚጠቁሙት ዶክተሩ፤ ይህም ህሙማኑ በእርዳታ የሚያገኙትን ገንዘብ ለውጭ አገር ህክምናው ለማዋል ከማሰብ ይልቅ ለዕለት ተዕለት ኑሮአቸው መደጎሚያና ለሚያሰቃያቸው ህመም ማስታገሻ የሚሆኑ መድኃኒቶች መግዣ እንዲውል በማድረግ፣ ዕለተ ሞታቸውን ይጠባበቃሉ ብለዋል፡፡ በየቤታቸው የሚበሉትና የሚቀምሱት የሌላቸውና በአገር ውስጥ ህክምና ሊድኑ በማይችሉ ከባድ የጤና ችግሮች ለተያዙ ህሙማን፤ በመቶ ሺዎች ዶላር የሚያስወጣ ህክምና በውጪ አገር ማድረግ እንደሚስፈልጋቸው መንገር ለህሙማኑ ተረት ተረት እንደማጫወት ነው የሚሉት ዶክተሩ፣ ህሙማኑ ይህን ያህል ገንዘብ ማግኘት የሚችሉበት አንዳችም ተስፋ የሌላቸው በመሆኑ፣ ከህመሙ በላይ የሚጎዳቸው “መቼ ይሆን የምሞተው” የሚለው ሃሳብና ጭንቀት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በስፋት ከሚታዩት የውጭ አገር ህክምና የገንዘብ እርዳታ ጠያቂዎች መካከል፣ ከ92 በመቶ በላይ የሚሆኑት ገንዘቡን አግኝተው በመታክም ከህመማቸው የመፈወስ እድል እንደሌላቸው ያመኑና በእርዳታ በሚያገኙት ገንዘብ ህይወታቸውን ለማቆየት የቆረጡ ናቸው ብለዋል፡፡
የልብ ህመም፣ የኩላሊት ድክመት (ከአገልግሎት ውጪ መሆን) ካንሰር፣ የአንጎል እጢና የአዕምሮ ህመሞች በአብዛኛው በአገር ውስጥ ህክምና ማዳን ባለመቻሉ የውጭ አገር ህክምናን የግድ የሚሉ የጤና እክሎች መሆናቸውን የሚናገሩት ዶክተሩ፤ እነዚህ የጤና ችግሮች በአሁኑ ጊዜ የበርካታ ኢትዮጵያዊያን ፈተናዎች እየሆኑ መምጣታቸውን ጠቁመዋል፡፡ “አሳሳቢው ጉዳይ በእነዚህ የጤና ችግሮች ተይዘው የወገኖቻቸውን የእርዳታ እጅ ከሚጠባበቁት ህሙማን መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት በወጣትነት ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎች መሆናቸው ነው፡፡
እነዚህ ወጣቶች በህይወት የመኖርና ያለመኖር ፍጥጫና ጉጉት ውስጥ ሆነው፣ ከህመማቸው ለመዳን ብቻ ሳይሆን ለጥቂት ቀናት በህይወት ለመቆየት የወገኖቻቸውን የእርዳታ እጆች ጠባቂ ሆነዋል፡፡ ይህ ደግሞ የሚያሳየን ነገ አገር ተረካቢ ይሆናሉ የምንላቸውን ወጣቶቻችንን በቀላሉ ሊድኑ በማይችሉ በሽታዎች እያጣናቸው መሆኑን ነው” ሲሉ ዶክተሩ ይናገራሉ፡፡
ዛሬ ዛሬ በመዲናችን የተለያዩ አካባቢዎች በብዛት የሚታዩት የውጭ አገር ህክምና ፈላጊ የእርዳታ ጠያቂዎች፤ ለህክምናው አስፈላጊ የሆነውን ገንዘብ ከማግኘታቸው በፊት ህይወታቸው እንደሚያልፍና በእርዳታ የሚሰበሰበው ገንዘብ የህክምና ወጪውን ለመሸፈን የማይበቃ መሆኑን ባደረጉት ጥናት ማረጋገጣቸውን ዶክተር ፍቃዱ ይገልፃሉ፡፡

Published in ዋናው ጤና

በኅዋ ላይ ጠፈርተኞች የሚገጥሟቸው ህመሞች
ወደ ኅዋ ከሚጓዙ መቶ ጠፈርተኞች መካከል 45ቱ በህመም ወይም በበሽታ ምልክቶች ይሰቃያሉ። እነዚህ ምልክቶች የማስመለስ፣ የራስ ምታት ወይም ማንኛውንም ነገር ለመስራትም ሆነ ለመደሰት ከመጠን ያለፈ አቅም ወይም ኃይል ማጣት (ሌተርጂ) ሊሆን ይችላል፡፡ ደግነቱ ግን ምልክቶቹ ከጥቂት ሰዓት በላይ አይቆዩም፡፡
እንባና ኅዋ
ኅዋ ወይም ጠፈር ላይ ያለ ሰው እጅግ መሪር ኀዘን ቢሰማው እንኳ ማዘን እንጂ እንባ አውጥቶ ማልቀስ አይችልም፡፡ ለምን ይመስልዎታል? መልሱን ፅሁፉ ሲጠናቀቅ ያገኙታል፡፡
ኅዋና ቁመት
በጀርባ በአጥንት ወይም አከርካሪ መካከል የሚገኙ ዲስኮችን፣ የስበት ኃይል (ግራቪቲ) ብዙ ጊዜ ወደታች ስለሚስባቸው መጠነኛ መጠጋጋት ይፈጠራል፡፡ ነገር ግን ጠፈርተኞች የሚኖሩትና የሚሰሩት ስበት በሌለበት ዜሮ ግራቪቲ አካባቢ ስለሆነ፣ በአከርካሪ አጥንታቸው መካከል የሚገኙት ዲስኮች መጠነኛ መስፋፋት ያደርጋሉ፡፡ ይህም ሁኔታ አከርካሪን ስለሚያስረዝም ጠፈርተኞቹ ቁመት እንዲጨምሩ ያደርጋል፡፡ የሚጨመረው ቁመት ከሰው ሰው የሚለያይ ቢሆንም 3 በመቶ የተለመደ ነው፡፡ ሰውየው ወይም ሴቲቱ በነበራቸው ቁመት ላይ ከ5-8 ሳ.ሜ ይጨምራሉ፡፡ ይህ ርዝመት ግን ቋሚ አይደለም፡፡ ጠፈርተኞቹ ወደ ምድር ሲመለሱ ግራቪቲ ስለሚጠብቃቸው ወደ ቀድሞ ቁመታቸው ይመለሳሉ፡፡
ሰዎች ስበት በሌለበት ዜሮ ግራቪቲ አካባቢ ሲቆዩ፣ ሌሎች የሚፈጠሩ አካላዊ ለውጦችም አሉ። እነሱም:- የአጥንት ክብደት መቀነስ፣ የጡንቻ መድከም (ቀደም ሲል መሸከም ይችል የነበረውን ክብደት ያህል ያለመቻል) የሰውነት ፈሳሽ ክፍፍል መለወጥና የልብ አሰራር (የካርዲዮቫስኩላር ሲስተም) ከተለመደው ውጭ መሆን ናቸው፡፡
ፀሐይ
ፀሐይ፤ በሚልኪ ዌይ (milky way) ውስጥ ከሚገኙ 200 ቢሊዮን ያህል ኮከቦች አንዷ ናት። እያንዳንዱ ኮከብ በአማካይ 16 መሬት መሰል ፕላኔቶች እንዳሏቸው ይገመታል፡፡
ንቦች ሁሉ ከምድረ ገጽ ቢጠፉ በሕይወት መኖር እንችላለን?  
እንዴታ! እኛ ሰዎች ንቦች ደግሞ በራሪ ነፍሳት፡፡ ምን አገናኘን? ዘር ማንዘራቸው ጥርግ ብሎ ቢጠፋ እንኳ እኛ እንኖራለን ይሉ ይሆናል፡፡ በእርግጥ እንኖራለን፡፡ ነገር ግን እንደተባለው ቀላል አይሆንም። ንቦች ትዝ የሚሉን ጣፋጭ የሆነውን ማራቸውን፣ ስንበላ ወይም በመድኃኒትነት ስንጠቀም አይደለም፡፡ ሲነድፉንና ኃይለኛ ህመሙ ሲሰማን ነው፡፡ ንቦች ግን ለበርካታ ዝርያዎች መኖር በጣም አስፈላጊ ናቸው። አንዳንድ ሰብሎችና ተክሎ ያለንቦች ዝርያቸውን አይተኩም፡፡
በምሳሌ እንይ፡፡ አየር ጤና አካባቢ ያለች ዘመዴ ግቢ ውስጥ አንድ የማንጎ ተክል ነበረች፡፡ ያቺ የማንጎ ተክል ወቅቷ ሲሆን በደንብ ታብባለች። ነገር ግን ፍሬ ወይም የሚበላ ማንጎ አታፈራም፡፡ ሶስት አራት ዓመት አይተው ምንም ቢያጡ “ሴቷ ናት አታፈራም” ብለው ነቅለው ጣሏት፡፡ ለምን መሰላችሁ ያላፈራችው? በሌላ አካባቢ ካለ ወንዴ የማንጎ ተክል አበባ ጣፋጭ ሲቀስም የተሸከመውን የወንድ ዘር ወደ ሴቷ የሚያደርስ (የሚያዳቅል) ንብ ስለጠፋ ነው፡፡
እንግዲህ ንቦች አዳቃይ (ፖሊኔተር) ናቸው ማለት ነው፡፡ በዓለም ላይ ከሚገኙ ሦስት ዝርያዎች የአንዱ አዳቃይ ንቦች ናቸው፡፡ ስለዚህ ንቦች ከምድረ ገጽ ቢጠፉ በጣም የምንወዳቸው ፖምና ብሮኮሊን.. ጨምሮ ከ130 በላይ ፍራፍሬና አትክልቶች በፍጥነት የመጥፋት አደጋ ያንዣብብባቸዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ለመዳቀል፣ ንቦችን የማይፈልጉት እንደ ስንዴ፣ ገብስ፣ በቆሎ… እና ጥቂት ያህል እህሎች ብቻ ይቀራሉ ማለት ነው፡፡
የንብ መንጋ ቁጥር በአስደንጋጭ ፍጥነት በመቀነስ ላይ መሆኑ ነው፡፡ ሳይንቲስቶች ምክንያቱን ለማወቅ ትግል ይዘዋል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ገበሬዎች ንቦች እንደሚያደርጉት ለማዳቀል፣ የአንዱን ሰብል አትክልት ወይም ፍራፍሬ አበባ (የዘር ፍሬ) በእጅ በሌላው ላይ መነስነስ ጀምረዋል፡፡ ይህ ተግባር ደግሞ ወጪው በጣም ብዙና አድካሚ ነው፡፡ ዓለም ያላትን የንብ ዝርያዎች ሙሉ በሙሉ ብታጣ መኖራችን አይቀርም፡፡ ነገር ግን ዓለም አሁን ያሏትን ጣፋጭ አትክልቶችና ፍራፍሬዎች ይዛ አትቀጥልም። የተለያዩ ሰብሎች ይዛ እንደምንኖርባት ዓለም የምትጥም ምድር አትሆንም፡፡
መልስ - ግራቪቲ
ዋቢ - (Science Uncovered July 2014)  

Published in ህብረተሰብ

ውድ እግዚአብሔር -
ባቢ ቢራ ጠጥቶ ሲመጣ አልወድም፡፡ አፉ መጥፎ መጥፎ ይሸታል፡፡ በዚያ ላይ ይጮህብኛል። አንተ ነህ ቢራ የፈጠርከው? ለምን?
ሳሚ - የ6 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር -
እሁድ እለት ሙሽሮቹ  ቤተክርስትያን ውስጥ ሲሳሳሙ አየኋቸው፡፡ ፈቅደህላቸው ነው?
ሮዝ - የ5 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር -
ካንተ የተሻለ ለእግዚአብሔርነት የሚሆን ያለ አይመስለኝም፡፡ እንዲህ ያልኩት እግዚአብሔር ስለሆንክ አይደለም፡፡ የእውነቴን ነው፡፡
ቻርልስ - የ7 ዓመት ህፃን  
ውድ እግዚአብሔር -
ዳይኖሰርን ባታጠፋው ኖሮ መኖር አንችልም  ነበር፡፡ ትክክል ነው ያደረግኸው፡፡  
ኤርሚ - የ7 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር -
በዓለም ላይ ያሉትን ሰዎች በሙሉ መውደድህ በጣም ያስደንቃል፡፡ እኛ ቤት አራት ሰዎች ብቻ ናቸው ያሉት፡፡ ሁሉንም መውደድ ግን አልቻልኩም፡፡
ናኒ - የ8 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር -
ሌሊት ሌሊት አስፈሪ ህልሞች አያለሁ። ከእነማሚ ጋር ልተኛ ስል አድገሃል ተባልኩ። አስፈሪ ህልሞች ከየት ነው የሚመጡት? ይሄ የሚመለከተው ሰይጣንን ነው አይደል?
ሔኖክ - የ6 ዓመት ህፃን

Published in ህብረተሰብ
Saturday, 31 May 2014 14:02

ገፅ ለገፅ

ተፋጠጥ፤ ተገላለጥ፣ ተሞራረድ፣ ችግር ፍታ!

          ባለፈው ሳምንት የጀመርኩት የደብረዘይት ገፅ ለገፅ (Interface meeting) ዛሬም ቀጥሏል። ህዝብና መንግስት ፊት ለፊት ተገናኝቶ የሚወያይበትና መሬት ላይ ላሉ ችግሮች መፍትሔ የሚሰጥበት በጣም ያስገረመኝ ውይይት ነው ብዬ ነበር፤ ባለፈው ሳምንት ጉዞ ማስታወሻዬ ላይ፡፡ ፕሮግራሙን የሚመሩት  
አቶ ግርማ ከበደ ለ16 ዓመት የማኔጅመንት ኢንስቲቲዩት ባልደረባ የነበሩ ሲሆኑ፤ ቆመው ሲናገሩ ቆይተው በኋላ ወንበር ይገባኛል ብለው ውይይቱን ተቀምጠው ሊመሩ ተሰየሙ፡፡ (ሁላችንንም ፈገግ አሰኙን) የእየሩሳሌ የህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት (ኢህማልድ) (የጄክዶ) የፕሮግራም ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ገፅ ለገፅ የመንግሥት የሪፎርም አጀንዳ መሆኑን ገለጡ፡፡ በዚህ ጉዳይ ኢህማልድ (ጄክዶ) ከፍተኛ ልምድ እንዳለው አብራሩ፡፡
በባህር ዳር መሰል ፕሮግራም መካሄዱንና በድሬደዋ፣ ከዚያም በአጄ ሻሸመኔ እንደሚካሄድ ገለፁ፡፡ የዕለቱን ጥናታዊ ማብራሪያ የሰጡት፤ አቶ ብርሃኑ ሰቦቃ ስለማህበራዊ ተጠያቂነት ፅንሰ-ሃሳብ እንደሚገልፁም አሳወቁ፡፡
አቶ ብርሃኑ ሰቦቃ የቢሾፍቱ ተሰብሳቢ ኦሮሚፋ ተናጋሪ ነው በሚል እሳቤ ይመስለኛል፤ “አርካፉኔ” በሚል ጀመሩና ቆይተው ይቅርታ ጠይቀው በአማርኛ ተያያዙት፡፡ “ሆኖም ያዘጋጀሁት በእንግሊዝኛ ነው” ብለው ቀጠሉ። ዛሬ፤ ትንሽ አዝናኑኝ፡፡ ኦሮሚፋ፣ አማርኛ፣ እንግሊዝኛ ዞሮ ዞሮ የምሁራን የጥናት ቋንቋ ናቸው፡፡
“የማህበረሰብ ተጠያቂነት ምንድነው? ለምንስ ይጠቅማል? የሚል ነው ነገሬ፡፡ በቀላሉ ስናየው ስልጣን በእጃቸው ያለ አካላት ለህዝቡ ለሚሰጡት አገልግሎት ተጠያቂ የሚሆኑበትና ምላሽ የሚሰጡበትን ኃላፊነት የሚያስቀይር ነገር ነው፡፡
ስለዚህም የህዝቡን ተሳትፎ የሚያሳይ ነገር ነው ማለት ነው፡፡ መብቱን የመጠየቅና ግዴታውን የመወጣት ነገርን ያካተተ ነው ማለት ነው፡፡
በዲሞክራቲክ አሠራር ለመሄድ የህገ መንግሥት አንቀጽ 12፤ መሠረቱ ይሄ ነው፡፡ በዚህ አካሄድ “የመንግሥት አሠራር በሙሉ ግልፅ ይሆናል፡፡ ጥሩ የሰራ ሊሸለም፣ መጥፎ ቢሰራ ሊጠየቅ ይገባዋል” ነው የሚለው መንፈሱ፡፡ ‹አንቀፅ 50 ላይ ደግሞ፤ አተገባበሩ ወደ ህዝቦች እንዲሆን ይደረጋል› ይላል፡፡ እነዚህን ወደመሬት ለማውረድ የተለያዩ ህጐች፣ ደንቦች፣ መመሪያዎች ወጥተዋል፡፡”
ይህንን መመርመር ነው እንግዲህ - የዚህ ስብሰባ ዋና ደርዝ፡፡
ሥራዎች ሲሰሩ በቅድሚያ ሰዎች አብረዋቸው መቀጠር አለባቸው፡፡ አለዛ ሥራ አይሠራም፡፡ አዕምሮን የማቃናት ፕሮግራም ያስፈልጋል፡፡ 10 ዓመቱ ነው ሲቪል ሰርቪስ ፕሮግራም! ከተጀመረ
ለተገልጋዩ ቀና አገልግሎት መስጠት ነው ሲቪል ሰርቪስ፡፡ ይሄን ሁሉ ግን መንግሥት ነው እየተቆጣጠረ ያለው፡፡ ህዝቡስ እንዴት ነው? ነው ጥያቄው፡፡ የተጠያቂነት ሁኔታ ለ18 ወራት ፓይለት (የፕሮጀክት ሙከራ) የነበረው እዚህጋ ይመጣል፡፡
ጥሩ ተሞክሮ ነበር፡፡ ተሞክሮውን ትመርጡታላችሁ? ተብሎ ነበር በ2008ቱ የኢሲኤ ስብሰባ የቀረበው፡፡ “የት ሄዳችሁ ነው ተሞክሮውን ማየት የምትፈልጉት?” ተባሉ ተሰብሳቢዎቹ፡፡ ግማሹ ካናዳ፣ ግማሹ አሜሪካ፣ ሌላው እንግሊዝ አለ፡፡ የፕሮግራም መሪዋ፤
“ግዴላችሁም እዚሁ አለ፡፡ እሩቅ አትሄዱም፡፡ ሻሸመኔ ሂዱ!” ነው ያለቻቸው፡፡
17 ዓመት ሙሉ የተተኛበት የትምህርት ለውጥ በ2 ዓመት ውስጥ ውጤቱ ታየ፡፡
የማህበራዊ ተጠያቂነት ጉዳይ፤ ውጤታማ፣ ፈጣን፣ ተጠያቂነት ያለበት አገልግሎት ለህዝቡ እንዲደርስ ማድረግ ነው፡፡ የመልካም አስተዳደር አካል መሆኑን ነው ይሄ የሚያሳየው፡፡”
በአቶ ብርሃኑ ሰቦቃ በቀረበው ትንተና መሠረት፤ መላ ጨመቁ (essence) በሚከተሉት 5 ነጥቦች ላይ ያጠነጠነ ነው፡፡
1) መሬት ላይ ያለውን ነገር አንስቶ መወያየት ማለትም ችግሩን ለመፍታት ተሳታፊነት 2) ምላሽ መስጠት 3) ግልፅነት፤ ለምሳሌ ለጤና፣ ለትምህርት፣ ወዘተ የተመደበውን ባጀት ማሳወቅ፣ የሚታይ ቦታ መለጠፍ 4) ተጠያቂነት 5) ውጤታማና ቀልጣፋ የመንግሥት አገልግሎት ማግኘት፡፡ ምሁሩ ነጥቦቹ የሚሰጡትን ውጤቶች ሲነቁጥ እነዚህን አምስት ፍሬ ጉዳዮች ህዝብና መንግስት አንድ ላይ ሆኖ ከተወያየባቸው፣ ከተፋጠጠባቸው፣ ከተሞራረደባቸውና ወደ ተግባራዊ መፍትሄ ከተሸጋገረባቸው፤ ሀ) ህዝብና መንግስት አንድ ቋንቋ ይናገራሉ፡፡ ድህነትን ለማስወገድም ይቆራኛሉ ለ) መረጃ ለሁሉም ይዳረሳል ሐ) ህዝብን ማብቃት (empower ማድረግ) ይቻላል፤ መ) ግልፅነትና ተጠያቂነት ወደ ልማት ያመራል፡፡

የትምህርት ነገር
ሌላው በከፍተኛ ደረጃ ለውይይት የቀረበው ጉዳይ “በትምህርት በኩል ያለው ችግር ምንድን ነው” የሚለው ነው፡፡ “የተማሪዎች የማንበብ ባህል መዳከምና የትምህርት ውጤታቸው በዚያው መጠን መጓተቱ ነው” የሚል ድምዳሜም ቀርቧል። Readers are great leaders (አንባቢዎች ታላላቅ መሪዎች ይሆናሉ እንደማለት ነው)
“የትምህርት ውጤትን በተመለከተ በተለይ ቋንቋና ሂሳብ ላይ ዝቅተኛ እርካታ ነው ያለው፤ ተብሏል፡፡ Transition rate (የማለፍ ዕድል መጠኑ ግን ጥሩ ነው፡፡) ከ8ኛ ወደ 9ኛ ማለት ነው። ትምህርት ሚኒስቴር 50 እና ከዚያ በላይ አቬሬጅ ያመጣ ነው የሚያልፈው እሚለውን ልብ አርጉ። ያንን አምጥቶ አደለም ያለፈው፡፡ በኋላ ወደ ዩኒቨርሲቲ ማለፊያ ሲቃረብ ወገቤን ሊል ይችላል። ብሾፍቱ እንደብሾፍቱ በትምህርት ዙሪያችን ካሬ አለው ግን የበለጠ መሠራት አለበት፡፡ በተለይ ከላይ ብራሪ፣ ከንባብ አጋዥ ማቴሪያሎችና ከመፃህፍት አኳያ መጠናከር አለበት፡፡ 1ኛ ደረጃ የብሾፍቱ የትምህርት ችግር የመፃህፍት ቤት አገልግሎት ነው፡፡ 2ኛ ደረጃ ጥራት ያለው መፃህፍት ዕጥረት ነው፡፡ 3ኛ ደረጃ ያስቀመጠው የሳይንስ ላቦራቶሪ እጥረትና የማቴሪያልም አለመኖር ነው፡፡ ስለዚህ የመማር አግባብ ተጎድቷል፡፡”
የጋራው ውይይት ሲቀጥል ችግር ብቻ ሳይሆን መፍትሔም መነሳቱ ደስ ይላል፡፡ በኢትዮጵያ በሁሉም ቦታ እንዲህ በግልፅ ገፅ በገፅ ነገሮች ቢነሱ እንዴት መልካም ነበር አልኩኝ፡፡ አንዱ አንዱ ላይ ጣት መጠቆም አይደለም፡፡ ችግሩን በጋራ አንስተን በጋራ ኃላፊነታችንን እንዴት እንወጣ የሚል መንፈስ እንዳለው” የፕሮግራም መሪው ገለፁ፡፡

የውሃ ነገር
የውሃ ችግርን በተመለከተ ሪዘርቯየር መተከል አለበት፡፡ በትምህርት ቤት ረገድ ከባለ ሀብቶችም ጋር ተወያይቶ የገንዘብ ማሰባሰብ መፍትሔ ይደረግ፡፡ በት/ቤት ቅፅር ስላሉ የመኖሪያ ቤቶች መንገድ ቢፈለግ፣ ከንቲባችንም እዚህ ስላሉ፣ መፍትሄ እንሻለት፡፡ በውሃ አለመኖር ምክንያት በትምህርት ቤቶች ከፍተኛ የፅዳት ችግር አለ፡፡ መልካም አስተዳደር ቃሉ ብቻ ሳይሆን ተግባሩም መኖር አለበት፡፡ የውሃ ችግር… የውሃ ችግር… (ብዙ ተወሳ፡፡) የቆሻሻ አንሺ መኪናን ችግር ለመፍታት የባለሀብቶች ተሳትፎ ምን መሆን አለበት?... የትምህርት ቤት ጉዳይ ላይ ከእኛስ ምን ይጠበቃል? የሚል መልዕክት ተላለፈ፡፡ ባለመብቶቹ አገልግሎት ተቀባዮች ናቸው መነሻችንም እነሱ ናቸው አሉ አቶ ብርሃኑ፡፡ አገልግሎት ሰጪዎች Defense አይደለም የምታካሂዱት፡፡ ይሄን ለመፍታት ምን ዝግጅት እያደረግን ነው፣ ካላደረግንስ በጋራ ምን ማድረግ አለብን? ወደሚል ነው መሄድ ያለብን፡፡ እየተገመገሙ ያሉት አገልግሎት ሰጪዎች ናቸው! ሀሳብ በነፃ እናንሸራሽር፡፡ አንዱ ጠያቂ አንዱ መላሽ መሆን የለበትም አሉ የፕሮግራም መሪው፡፡ ቀጥሎ ከመንግስት ወገን ያሉ አገልግሎት ሰጪዎች መናገር ጀመሩ፡፡ “አገልግሎት ሰጪው ምን እያደረገ ነው ህዝቡስ ምን ምላሽ እየሰጠ ነው እንድንባባል መቻላችን ትልቅ ነገር ነው” ብለው ጀመሩ፡፡
ይቀጥላል


Published in ህብረተሰብ

“በጐ ሰዎችን በመሸለምና በማክበር ሌሎች በጐ ሰሪዎችን እንፍጠር” በሚል ዓላማ በሀገራችን በጐ የሠሩትን የማመስገን ባህልን ለማበረታታት፣ ሀገራዊ አርአያዎችን ለመፍጠርና ለጀግኖቻችንም ዕውቅና የመስጠት  ልማድን ለማጐልበት በሚል የተጀመረው “የበጐ ሰው ሽልማት” የዘንድሮ ተሸላሚዎችን ግንቦት 30 እንደሚያሳውቅ ኮሚቴው ገለፀ፡፡
የ“በጐ ሰው ሽልማት” ዙር ሥነስርዓት በኢሊሌ ሆቴል እንደሚካሄድም ታውቋል፡፡ የዘንድሮው ሽልማት በሰባት ዘርፎች የሚሰጥ ሲሆን በሰላም፣ በሀገራዊ ዕርቅና ማህበራዊ አገልግሎት፣ በእርዳታና ሰብዓዊ ሥራ፣ በኪነ ጥበብ፣ በግብርናና ኢንዱስትሪ፣ በመንግስታዊ የሥራ ተቋማት ኃላፊነት፣ በቅርስ፣ ባህልና ቱሪዝም፣ እንዲሁም በጥናትና ምርምር ዘርፎች ከመቶ በላይ እጩዎች ቀርበው፣ 35 እጩዎች ተመርጠዋል፡፡
በየዘርፉ በተመደቡ ዳኞችም ሰባቱ የሽልማቱ አሸናፊዎች ይለያሉ ተብሏል፡፡
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው በሽልማቱና አጠቃላይ እንቅስቃሴው ዙሪያ ከሽልማት ኮሚቴው ሰብሳቢ ከደራሲ ዳንኤል ክብረት ጋር የአፍታ ቆይታ አድርጋለች፡፡


“የበጐ ሰው ሽልማት” እንዴት ነው የተጀመረው?
“የበጐ ሰው ሽልማት” የተጀመረው ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ ነው፡፡ ምክንያት የሆነው ደግሞ “የዳንኤል እይታዎች ጦማር” ሲከበር የነበረው ኮሚቴ፣ “ለአገር በጐ የሠሩ ሰዎችንስ ለምን አንሸልምም?” የሚል ሃሳብ በማንሳቱ ነው፡፡ እናም አምና በ2005 አምስት ሰዎች ከተለያዩ ዘርፎች ተሸለሙ፡፡ እነዚያ ሰዎች መሸለማቸው በብዙዎች ዘንድ መነቃቃትን ፈጠረ፡፡ እሱን መሰረት አድርጐ ኮሚቴው በተጠናከረ ሁኔታ ከጦማር ውጪ ራሱን ችሎ እንዲንቀሳቀስ ተደረገ፡፡ ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ ነው የሽልማት ሥነስርዓቱን የሚያካሂደው፡፡
የዳንኤል እይታዎች ጦማርና “የበጐ ሰው ሽልማት” የሚያገናኛቸው ነገር አለ?
የሚያገናኛቸው በምክንያትነት ያስጀመረው የጦማሩ በዓል በመሆኑ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ የተለያዩ አንባቢያን ለእጩዎች ድምፅ እንዲሰጡ ቅስቀሳ የተደረገው በጦማሩ ነው፡፡ በእርግጥ በማህበራዊ ድረ ገፆች፣ በኤፍኤም የሬዲዮ ጣቢያዎችና በህትመት ውጤቶችም ተካሂዷል፡፡ ከዚህ በቀር ግን ሁለቱን የማያገናኛቸው ነገር የለም፡፡
የ2005 “የዓመቱ በጐ ሰው” ተሸላሚዎች እነማን ነበሩ?
አምስት ናቸው፡፡ ከመገናኛ ብዙኃን መዓዛ ብሩ ስትሸለም፣ በእርዳታና ሰብዓዊ ስራ ቢኒያም፣ (የመቆዶኒያው  ስራ አስኪያጅ) ተሸልሟል፡፡ ንባብን በማበረታታትና በተለይ መጽሐፍ ገዝተው ማንበብ የማይችሉ ሰዎች በቀላሉ ማንበብ የሚችሉበትን መንገድ በመፍጠሩ፣ ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ በኪነጥበብ ዘርፍ ሊሸለም በቅቷል፡፡ አዲስ የንግድ አሰራር ዘዴን በመቀየስና በመምራት ዶ/ር እሌኒ      ገ/መድህን፣ የኢትዮጵያን ታሪክና ባህል፣ እንዲሁም ጥንታዊ ቅርሶች በመጠበቅ በሰሩት ስራ ደግሞ ንዑረድ ተፈራ መልሴ ተሸልመዋል፡፡
ሽልማቱ የመንግስት ባለስልጣናትንና ፖለቲከኞችን ያካትታል?
ሽልማቱ እስከ አሁን ባለስልጣናትንና ፖለቲከኞችን አላካተተም፡፡ ግን በመንግስት ስራ ላይ ተመድበው ያከናወኗቸውን ሥራዎችና የተሰጣቸውን ሃላፊነት ምን ያህል ተወጥተዋል የሚለውን በማየት፣ ማህበረሰቡን ያገለገሉ ሰዎች የሚሸለሙበት ዘርፍ አለ፡፡
የባለፈው ሽልማት ምን ነበር? የዘንድሮስ? የገንዘብ ምንጫችሁ ምንድነው?
ዓምና “የበጐ ሰው ዓመታዊ ሽልማት” የሚል ሰርተፍኬት ነበር የሰጠነው፡፡ ዘንድሮ ግን ራሱን የቻለ ሽልማት ተዘጋጅቶለታል፡፡ ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ ናቸው የበጐ ሰው ሽልማት የሚል እንደ ኦስካር ዓይነት ሽልማት በራሳቸው ዲዛይን ሰርተው ያዘጋጁት፡፡ እስከ አሁን ድረስ ስራውን እየሰራን የነበረው የኮሚቴው አባላት በምናዋጣው ገንዘብ ነው፡፡ አሁን ግን ዳሽን ቢራ ሥራችንን እንደሚደግፈን ቃል ገብቶ ከእኛ ጋር እየሰራ ነው፡፡
እንደዚህ ዓይነት ሽልማቶች የአንድ ጊዜ ዜና ብቻ ሆነው ይቀራሉ፣ ቀጣይነቱ ታስቦበታል?
አዎ!! በቀጣይ “የበጐ ሰው ሽልማት” የበጐ አድራጐት ድርጅት ፈቃድ አውጥቶ፣ ራሱን ችሎ እንዲቀጥል ለማድረግ አስበናል፡፡ አምና በጠባቡ ሰራነው፤ ዘንድሮ ከፍ አደረግነው፡፡ በቀጣይ ደግሞ አገር አቀፍ ሆኖ የሚካሄድበትን መንገድ እያጠናን ነው፡፡
የ2006 “የበጐ ሰው ሽልማት” እጩዎች
በኪነጥበብ ዘርፍ
ሙላቱ አስታጥቄ፣
ተስፋዬ አበበ
አባባ ተስፋዬ ሳሕሉ
ይልማ ሀብተየስ
ታደሰ መስፍን
በማኅበራዊ አገልግሎት
ዶ/ር አበበ በጂጋ
ዶ/ር ሚናስ ኅሩይ
ቄስ አሰፋ ሰጠኝ (ትግራይ)
ብጹዕ አቡነ ዮናስ (አፋር)
ደበበ ኃይለ ገብርኤል
በእርዳታና ሰብአዊ ሥራ
ዶ/ር ተዋበች ቢሻው
ዶ/ር በላይ አበጋዝ
ወ/ት ሮማን መስፍን
ሲ/ር ዘቢደር ዘውዴ
ወ/ሮ አበበች ጐበና
በግብርና፣ ኢንዱስትሪና ኢንተርፕርነርሺፕ
ቤተልሔም ጥላሁን
ዶ/ር ኢንጂነር ዳንኤል ቅጣው
ዶ/ር ወሬታው በዛብህ
አሶሴሽን ኦፍ ውሜን ኢን ቢዝነስ
ካፒቴን ሰሎሞን ግዛው
መንግሥታዊ ኃላፊነትን በመወጣት
አምባሳደር ቆንጅት ሥነ ጊዮርጊስ
ኢንጅነር ስመኘው በቀለ
አቶ በድሉ አሰፋ
አቶ ይርጋ ታደሰ
አቶ አድማሱ ታደሰ
በቅርስ፣ ባሕልና ቱሪዝም
አቶ ዓለሙ አጋ
አቶ ሀብተ ሥላሴ ታፈሰ
ሼህ አብዱላሂ ሸሪፍ
ዶ/ር ዘረ ሠናይ ዓለም ሰገድ
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለ አደራ ማኅበር
በጥናትና ምርምር ዘርፍ
አምባሳደር ዘውዴ ረታ
ፕ/ር አሠራት ኃይሉ
ፕ/ር ዓለም ፀሐይ መኮንን

Published in ህብረተሰብ
Saturday, 31 May 2014 13:59

‘የጎንዮሽ ጣጣ’…

ማስታወቂያዎች ከመተላለፋቸው በፊት “ብታምኑም ባታምኑም” ተብሎ ይፃፍልን

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እኔ የምለው… ሀዲዱን እየነቀሉት ነው የሚባለው እውነት ነው እንዴ? ለነገሩ መገረም ስለተውን “ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም…” ምናምን አይነት ተረት ትተናል፡፡ አሀ፣ ልክ ነዋ… አምናና ካቻምና “ጉድ!” ያሰኙ የነበሩ ነገሮች ዘንድሮ ልዩ መለያዎቻችን (“ከአፍሪካ ቀዳሚ…” ምናምን የሚባለው አይነት) እየሆኑ ነዋ!
ይሄ የዓለም ዋንጫ መጥቶ ለጥቂት ሳምንታት ለ‘ስታንድ አፕ ኮሜዲያኖች’ ብቻ የሚሆኑ ዜናዎች ከመስማት ትንሽ ተንፈስ ባደረገን! እኔ የምለው…ይሄ የኳስ ፍቅር ነገር…ይቺን ስሙኝማ…
የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ጨዋታ ነው፡፡ ያው እንግዲህ ትኬቶች የወንበር ቁጥር ያላቸው ናቸው፡፡ አንዱ የተከዘ ሰውዬ ከተቀመጠበት ጎን ያለ ወንበር ባዶ ነው፡፡ በወዲያኛው ወገን ያለው ተመልካች “ምን አይነት ሰው ነው በዚህ የፍጻሜ ጨዋታ ዕለት የሚቀረው!” ይላል፡፡ የተከዘው ሰውዬም “ለሚስቴ የተያዘ ቦታ ነበር፡፡ ያለፉትን አምስት የዓለም ዋንጫዎች የፍጻሜ ጨዋታዎች አይተናል፡፡”
“አሁን ታዲያ ምነው አልመጣችም?”
“ህይወቷ ስላለፈ ነው፡፡”
በጣም አዝናለሁ፡፡ ግን ሌላ የቤተሰቡ አባል ወይም ጓደኛ መምጣት አይችልም ነበር?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ሰውየው ምን ቢል ጥሩ ነው…
“አይችልም፣ ሁሉም እሷ ቀብር ላይ ናቸው፡፡”
የኳስ ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…ዓለም ባለቀች በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ነው፡፡ በመንግሥተ ሰማያትና በገሀነም መካከል የድንበር ውዝግብ ይነሳል፡፡ ነገሩን በሰላም ለመጨረስ እግዚአብሔር ዲያብሎስን ለጠረዼዛ ዙሪያ ድርድር ይጋብዘዋል፡፡ ዲያብሎስም በመንግሥተ ሰማያትና በገሀነም መካከል የእግር ኳስ ግጥሚያ እንዲደረግ ሀሳብ ያቀርባል፡፡
እግዚአብሔርም… “እሱ እንኳን ቢቀርብህ አይሻልም! ጎበዝ ተጫዋቾች በሙሉ መንግሥተ ሰማያት እንደሚገቡ አታውቅም?” ይለዋል፡፡
ዲያብሎስ ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው…“እሱስ ልክ ነህ፣ ግን የእግር ኳስ ዳኞች በሙሉ ገሀነም ናቸው፡፡”
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… የመድኃኒቶች አጠቃቀም ዝርዝር ላይ ‘ሳይድ ኢፌክትስ’ ምናምን የሚባል ሊከሰቱ ስለሚችሉ የጎንዮሽ ውጤቶች (‘የጎንዮሽ ጣጣ’ ማለትም ይቻላል፣) የሚጻፉ ነገሮች አሉ አይደል…በሌላውም ነገር ሁሉ እንዲሁ ይደረግልን፡፡ ነገሮች የሚያስከትሉትን ‘የጎንዮሽ ጣጣ’ ሳናውቅ እየቀረን ተቸገርና!
ሀሳብ አለን…“ተከታዩን ዜና በመስማት፣ በማንበብ ወይም በመመልከት ለሚከተሉ ‘የጎንዮሽ ጣጣዎች’ ኃላፊነት የማንወስድ መሆናችንን እናስታውቃለን፣” ምናምን የሚባል ነገር አብሮ ይተላለፍልንማ!
እናማ… “ሊከሰቱ ከሚችሉ የጎንዮሽ ጣጣዎች መካከል…
የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣
ዜና አቅራቢውን ጠምዶ መያዝ…” ምናምን እየተባለ ቢዘረዘርልን፡፡
የምር እኮ ዘንድሮ አንዳንድ ‘ዜና’ እየተባሉ የሚቀርቡ ነገሮች… አለ አይደል… ገና ስንሰማቸው ወይም ስናነባቸው የኦክሲጅን እጥረት ሊገጥመን ይችላል!
“ማስጠንቀቂያ፡— ይህን ጽሁፍ ከምግብ በፊት ማንበብ በምግብ መፈጨቱ ሂደት ላይ ለሚፈጥረው ማንኛውም አይነት ችግር የማንጠየቅ መሆኑን እናስታውቃለን፣” የሚልም ይካተትልን፡፡
ደግሞላችሁ… ‘ዘጋቢ’ ፊልሞችን በተመለከተ ሀሳብ አለን፡፡
“ማስጠንቀቂያ፡— ይህን ዘጋቢ ፊልም በማየት ለሚፈጠረው ድብርት ወይም ሕይወትን የመጥላት ስሜት…ኃላፊነቱ የተመልካቹና የተመልካቹ ብቻ ነው፣” ተብሎ ይጻፍልንማ! እንዲህ ብሎ መገላገል እያለ ‘ዘጋቢ ፊልም’ ባየን ቁጥር እኛም “እነዚህ ሰዎች አሁንም ዋሻ ግድግዳ ላይ ስዕል ይስሉ ከነበሩ ቅመ አያቶቻቻን የተሻለ ላያስቡ ነው!” ምናምን እያልን ባልተዘባበትን ነበር፡፡
ስሙኝማ…መቼም እዚህ አገር ‘ተመሳስሎ’ ያልተሠራ ነገር ማግኘት አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡ እኔ የምለው…እግረ መንገዴን የሆነ ነገር ትዝ ብሎኝ ነው፡፡ ምነዋ እስካሁን ድረስ “እነ እከሌ የእንትንን ምርት አስመስለው ሲሠሩ ስለተገኙ ሀግ ፊት ቀርበው…” ምናምን የሚባል ነገር የማንሰማሳ!
እናላችሁ…‘ተመሳስለው ከተሠሩ ፈገግታዎችና ሳቆች ራስን መጠበቂያ አሥር ዘዴዎች’ የሚል የስነ ልቡና መጽሐፍ ይውጣልንማ! ልክ ነዋ…ጠቅላላ ህዝቤ እንደ ፕላስቲክ ተለጥጦ ድርግም የሚል ፈገግታ እያሳየ ‘የጎንዮሽ ጣጣዎቹን’ እንዳናይ እየተሞኘን ነዋ! አንድ በጣም ፈገግ የሚሉ ሰዎች ሲገጥሙት አንድ ሺህ አንድ ጥርጣሬዎች የሚሰፍሩበት ወዳጅ አለን፡፡ በደህናው ዘመን “ጨለምተኛ!” ምናምን ይባል ነበር፡፡ እንደ ዘንድሮ አያያዛችን ከሆነ ግን… “እውነቱን ነው፣ እንኳንም ተጠራጠረ!” የሚያሰኝ ነው፡፡
እንግዲህ ጨዋታም አይደል…“ተመሳስለው ከተሠሩ ‘ታሪኮች’ ራሳችሁን ጠብቁ…” የሚል ማሳሰቢያ በሆነ ነገር ላይ ታትሞ ይውጣልን፣ ወይ እንደ ‘ሲንግል’ ይለቀቅልንማ! አሀ…ሌሎች ያሉትን እየሰሙ፣ የጻፉትን እያነበቡ… አለ አይደል… የራስን ታሪክ ‘ቆርጦ መቀጠል’ በዛ!
“የማንበብ ፍቅር ያሳደረብኝ የአምስተኛ ክፍል የአማርኛ አስተማሪዬ…” (‘የማንበብ ፍቅር’ የተባለው እኮ በዓመት ሁለት ሙሉ ለሙሉ የተነበቡና ሁለት ግማሽ ላይ የተቋረጡ መጽሐፍት ናቸው!)
“የባዮሎጂ አስተማሪዬ የሳይንስ ፍቅር አሳድሮብኛል…”
“በልጅነቴ የሻኪራን ዘፈኖች እወድ ነበር…” (ያኔ እኮ ሻኪራ፣ አይደለም ልትወለድ እናትና አባቷ በእሷ ወደዓለም መምጣት ስለሚጠናቀቀው እነሆ በረከት ጉዳይ ገና ድርድር እንኳን አልጀመሩም፡፡)
ደግሞላችሁ…“ተመሳስለው ከሚገቡ እንግሊዘኛ ቃላቶች ራሳችሁን ጠብቁ…” ይባልልንማ! አለ አይደል…
“ኢንተረስቲንግ ነኝ…”
“ኮንፊዴንሺያል ነኝ…”
የመሳሰሉትን ለማለት ነው፡፡ የምር ግን አንዳንዴ፣ አይደለም በየድራፍቱ ላይ.. በኤፍ ኤሞች ላይ የምንሰማቸው ተመሳስለው የሚገቡ የ‘እንግሊዝኛ’ ቃላት ነገር…‘የፈረንጅ አፍ’ የሚያውቁት ሰዎች እንዴት እንደሚሸማቀቁብን እነሱ ብቻ ናቸው የሚያወቁት፡፡
እኔ የምለው… እግረ መንገዴን የሆነ ነገር ትዝ ብሎኝ ነው፣ ከዚህ በፊት ተብሎ ከነበረም ልድገመው…አንዳንድ ሙያዎች የማህበራቱ ብዛት ከባለሙያዎቹ ብዛት ጋር ሊስተካከል ነው እንዴ!! ልክ ነዋ…ለምሳሌ ጋዜጠኝነትን ውሰዱልኝ፡፡ አለ አይደል…እንደ ማህበራቱ ብዛት ቁጥራችንም ያን ያህል ከሆነ…ለእኛ ብቻ እኮ ራሱን የቻለ ‘የህዝብ ቆጠራ’ ነገር ሊያስፈልገን ነው!  አሀ… አንድ  ግለሰብ ፌስቡክ ላይ አምስት ሺህ ፍሬንዶች ካሉት አንድ ማህበርም መቼም አንድ ሦስት ሺህ ያህል አባላት አያጣም፡፡ እናማ…በአሥር ሺዎች ብንገባ አይገርምማ!
ሀሳብ አለን…ይሄን ቦታ ይከለልልንማ! (የስፖርት ጋዜጠኞች የራሳቸው ‘ቁራጭ መሬት’ ይሰጣቸዋል— ከግዴታ ጋር፡፡ አሀ…ልክ ነዋ…  ማንቼ፣ አርሴ የሚባሉትን ነገሮች ከድንበራቸው ካሳለፉ በሌሎች ጋዜጠኞች ላይ እንደ ጥቃት ተቆጥሮ በእነሱ ክልል የኢንተርኔት አገልግሎት ይቋረጣል፡፡ ቂ…ቂ…ቂ… ኢንተርኔት ቢቋረጥ ምን እንደሚውጠን አንድዬ ይወቀው!)
ማስታወቂያ ላይ ሀሳብ አለን…ማስታወቂያዎች ከመተላለፋቸው በፊት በትልቁ ‘ብታምኑም ባታምኑም’ ተብሎ ይጻፍልን፡፡
እናማ…በሁሉም ነገሮች ላይ ‘የጎንዮሽ ጣጣዎች’ ይነገሩንማ!
“እንትና የተባለውን ቦተሊከኛ ዲስኩር በመስማት ለሚፈጠረው የአእምሮ ብቃት ማነስ ‘የጎንዮሽ ጣጣ ተጠያቂ አለመሆናችንን እያስታወቅን ‘የቦተሊከኛው ንግግር ትልቁን አንጀቴን ከነበረበት ወዴት እንደሰወረብኝ ይጠየቅልኝ…’ አይነት አቤቱታ የማንቀበል መሆኑን እናሳውቃለን፡፡
‘የጎንዮሽ ጣጣ’ ከሚያስከትሉ ነገሮች አንድዬ ይሰውራችሁማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Published in ህብረተሰብ
Saturday, 31 May 2014 13:56

የፖለቲካ ጥግ

ልበሰለ ፖለቲከኛ ስለቀጣዩ ምርጫ ሲያስብ፣ የበሰለ ፖለቲከኛ ስለቀጣዩ ትውልድ ያስባል፡፡
 ጄምስ ፍሪማን ክላርክ-
መጥፎ ባለስልጣናት የሚመረጡት ድምፅ በማይሰጡ መልካም ዜጐች ነው፡፡
 ጆርጅ ዣን ናታን-
ትናንሾቹን ሌቦች አንገታቸውን ለገመድ እየሰጠን፣ትላልቆቹን ሌቦች ለመንግስት ሥልጣን እንሾማቸዋለን፡፡
           ኤዞፕ
ፈጣሪ  ድምፅ እንድንሰጥ ቢፈልግ ኖሮ እጩዎችን ያቀርብልን ነበር፡፡
ጄይ ሌኖ
ፖለቲካ እንደ ጦርነት የሚረብሽ ብቻ ሳይሆን ከጦርነትም የበለጠ አደገኛ ነው፡፡ በጦርነት አንዴ ብቻ ነው የምትገደለው፡፡ በፖለቲካ ግን ብዙ ጊዜ ትገደላለህ፡፡
 ዊንስተን ቸርችል
ፖለቲካ ደም መፋሰስ የሌለበት ጦርነት ሲሆን  ጦርነት ደም መፋሰስ ያለበት ፖለቲካ ነው፡፡
ማኦ ዜዶንግ  
ለአሜሪካ ፕሬዚዳንትነት ሁለት እጩዎች ብቻ በሚቀርቡባት አገር፣ እንዴት ለሚስ አሜሪካ 50 እጩዎች ይቀርባሉ?
 ያልታወቀ ደራሲ

“የኢህአዴግ የግንቦት 20 ፍሬዎች፣ ከእኛ የግንቦት 20 ፍሬዎች ይለያሉ” ተቃዋሚዎች
የግንቦት 20 አከባበር ጥበባዊ ፈጠራ ይጎድለዋል ተባለ

     የግንቦት ልደታ ከጠባች ጀምሮ ኢቴቪ የግንቦት 20 ፍሬዎችን እያስኮመኮመን ይገኛል - አንዳንዴ በግጥም አንዳንዴ በዜማ፡፡ ይሄስ ባልከፋ፡፡ ሁሌም ግርም የሚለኝ ግን በየግንቦት 20ው በዓል ስማቸው ሳይጠቀስ የማይታለፈው የኃይለሥላሴና የደርግ መንግስታት ናቸው፡፡ (እንዴት ዕድለኛ ቢሆኑ ነው?!) እኔ የምለው…በዓሉ የእነሱ ነው ወይስ የኢህአዴግ? (የእኛ ማለቴ ነው?)
ሌላው ደግሞ ምን መሰላችሁ? የበዓሉ አከባበር የፈጠራ ድርቀት ይታይበታል፡፡ አዎ ጥበባዊ ፈጠራ ይጐድለዋል፡፡ የደርግ ዓይነት ሥርዓት ተመልሶ እንዳይመጣ ቀኑን መዘከሩ ተገቢ ነው። ነገር ግን በፕሮፖጋንዳ የተሞላ በዓል መሆን የለበትም። እንደኔ እንደኔ ፕሮፓጋንዳውን ኪነ-ጥበብ ብትተካው ይሻላል፡፡ በፊልም፣ በትያትር፣ በስዕል፣ በሙዚቃ ወዘተ… ቢዘከር የበለጠ ውጤታማ በዓል እንደሚሆን አልጠራጠርም፡፡ (በቀይ ሽብር ዙሪያ የረባ ፊልም እኮ አልተሰራም!) የአሁኑ አንዴ አልፏል፡፡ ለመጪው ግንቦት 20 ማለቴ ነው፡፡
እስቲ አስቡት… ከመጀመርያው የግንቦት 20 በዓል ጀምሮ ሰዎች ያለፉትን ጨቋኝ መንግስታት ሲረግሙና በቁጭት ሲብከነከኑ ብቻ ነው ኢቴቪ የሚያሳዩ፡፡ (ድብቅ አጀንዳ አለው እንዴ?) ከተገረሰሰ 23 ዓመት የሞላው ደርግና ከንግስናቸው ከወረዱ 40 ዓመት ያለፋቸው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ እየተኮነኑና እየተረገሙ ነው ግንቦት 20 የሚከበረው - ዛሬም ከ20 ዓመት በኋላ!! (ቀላል የCreativity ችግር አለ?!) ቀኑ የእርግማን ነው የምርቃት? የምናከብረው የትላንትናን ጭቆና ነው ወይስ የዛሬን ነፃነት? ፈጣን የካድሬ መልስ አልቀበልም፡፡ ጥያቄው በደንብ ማሰብ ይፈልጋል፡፡ መበሻሸቅ ሳይሆን መወያየት ባህላችን ሊሆን ይገባል፡፡ (ብሽሽቅ ለፌስቡክ ፖለቲከኞች!)
መቼም ሰዎች (ያውም አዛውንቶች!) በኢቴቪ እየቀረቡ…. ተበድለን፣ ተገርፈን፣ ተጨቁነን፣ ታስረን፣ ታፍነን፣ ተገድለን ወዘተ … እያሉ የደረሰባቸውን ሲተርኩ ወደድንም ጠላንም ሃዘንና ድብርት ውስጥ መግባታችን አይቀርም፡፡ በየራሳችን ክፉ ትዝታም መቆዘም እንጀምራለን፡፡ (ይሄ ሁሉ ቅጣት በየትኛው ኃጢያታችን ነው?)
እኔ የምለው… ግንቦት 20ን በተሻለ የደስታና የመነቃቃት ስሜት መዘከር አንችልም እንዴ? (ድሉ እያለ አከባበሩን አልቻልንበትም!) ኢህአዴግ፤ “አመለካከት ላይ መሰራት አለበት” የሚለው ለካ ወዶ አይደለም! (የግንቦት 20 አከባበራችን የአመለካከታችን ውጤት ነው!) ይኸውላችሁ… ኢትዮ ቴሌኮም በቴክስት ሜሴጅ የላከው የግንቦት 20 የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት እንኳን “…Wishes all Ethiopian People a Happy Ginbot 20 Anniversary, the downfall of Dergue regime!” ነው የሚለው (ፍርጃ እኮ ነው!)
እንግዲህ 23 ዓመት ሙሉ “ደርግ የተገረሰሰበት የግንቦት 20 በዓል” እንጂ “ኢህአዴግ ድል ያደረገበት የግንቦት 20 በዓል” ሲባል ሰምተን አናውቅም፡፡ (ድል ላይ ሳይሆን ጠላት ላይ የማነጣጠር አባዜያችን እኮ ነው!) ምናለበት ክፉው ላይ ሳይሆን በጎው ላይ፣ ድህነት ላይ ሳይሆን ብልፅግና ላይ፣ ድንቁርና ላይ ሳይሆን ትምህርት ላይ፣ ነውጥ ላይ ሳይሆን ሰላም ላይ ኋላቀርነት ላይ ሳይሆን ሥልጣን ላይ ወዘተ ብናተኩር?!!
እኔ የምናፍቀው ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? ኢህአዴግ አንድም የጠላት ስም ሳያነሳ (የጥንትም የዛሬም ማለቴ ነው!) ግንቦት 20ን በሰላምና በፍቅር ስሜት የሚያከብርበትን ዕለት ነው!! (“ፀረ - ልማት ሃይሎች” ሳይባል እኮ ግንቦት 20ን ማክበር ይቻላል!)
የእስካሁኑን መንደርደርያ እንደ ግንቦት 20 ዲስኩር ቁጠሩልኝና ወደ ዋናው የዕለቱ ርዕስ ጉዳይ ልግባ፡፡ ለነገሩ የዕለቱም ርዕሰ ጉዳይ በግንቦት 20 ዙርያ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በግንቦት 20 ፍሬዎች ላይ ያነጣጥራል፡፡ እናላችሁ…23ኛውን የግንቦት 20 በዓል አስመልክቶ ኢህአዴግ “የግንቦት 20 ፍሬዎች” በሚላቸው ላይ አንዳንድ ቅሬታዎች (ኧረ ተቃውሞዎችም ናቸው!) እየተሰነዘሩ ነው። መሰንዘር ብቻም ሳይሆን የኢህአዴግ የግንቦት 20 ፍሬዎች ለራሱ እንጂ ለእኛ ምናችን ነው የሚሉ ወገኖች አሉ። እናም እነዚህ ወገኖች… “ሁሉም የየራሱን የግንቦት 20 ፍሬዎች ለምን አይናገርም?” ባይ ናቸው፡፡ ያው በአሁኑ ተጨባጭ ሁኔታ ደግሞ ሁሉም የየራሱን የግንቦት 20 ፍሬዎች በኢቴቪ መናገር የሚችልበት ዕድል እንደሰበዝ የሰለለ መሆኑ ይታወቃል (ለአውራው ፓርቲም አልበቃ እኮ!) ይሄንን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ሁለት ከተቃዋሚው ጐራ፣ ሁለት ደግሞ ከመንግስት ጐራ የተሰለፉ ወገኖች የግንቦት 20 ፍሬዎች የሚሏቸውን በዛሬው ፅሁፌ አቀርባለሁ (ይሄም ራሱ የግንቦት 20 ፍሬ መሆኑን ልብ ይሏል!) እናም ከእስከዛሬው ንግግራቸውና አቋማቸው ተነስቼ፣ የግንቦት 20 ፍሬዎቻችን የሚሏቸውን እንዲህ ከትቤላቸዋለሁ፡፡ (በእውነታ ላይ የተመሰረተ ምናብ ወለድ ልትሉት ትችላላችሁ!)
ከአገር ውስጥ ተቃዋሚዎች እጀምራለሁ፡፡
የግንቦት 20 ፍሬዎች - ለተቃዋሚዎች
መቼም እዚች ምስኪን አገር ላይ ከሚያስማሙን ነገሮች ይልቅ የማያስማሙን ነገሮች ይበዛሉ፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ሰሞኑን ኢቴቪና ኢህአዴግ መራሹ መንግስት፤ የግንቦት 20 ፍሬዎች እያሉ የሚደሰኩሩት ነገር እምብዛም የሚያስማማን አይደለም፡፡ (“ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ” አሉ!) እርግጥ ነው ኢቴቪ የግንቦት 20 ፍሬዎች የሚላቸው…ለራሱ ለኢቴቪና ለኢህአዴግ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ (ኢቴቪ ብቻ ለሚያውቃት ኢትዮጵያም ይሰራል!) እኛንና ህዝባችንን ግን ጨርሶ ሊወክል አይችልም፡፡
ኢቴቪ ለምን ጐበዝ ከሆነ… ሁሉም የየራሱን የግንቦት 20 ፍሬዎች እንዲናገር ዕድሉን አይሰጥም? (የእነሱን ፍሬዎች እንደማንጋራ ያውቀዋላ!) ሃቁን ለመናገር ኢቴቪ እስኪታክተን ድረስ የሚደሰኩርልን ባለሁለት ዲጂት የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የዜጐች ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር፣ የህዝቦች እኩል ተጠቃሚነት፣ የፕሬስ ነፃነት፣ ልማት፣ ብልፅግና፣ ወዘተ ሁሉ የሚገኙት በኢቴቪ ስክሪንና በኢህአዴግ “የምኞት ቋት ውስጥ” ብቻ ነው፡፡ የኢህአዴግ የግንቦት 20 ፍሬዎች አይመለከተንም ብንልም የራሳችን የግንቦት 20 ፍሬዎች የሉንም ማለት ግን አይደለም፡፡ በደንብ አሉን እንጂ! (የራሳችን እያለን የሌላውን አንጋራም!) እናም እነ ኢህአዴግ የሚሰማ ጆሮ ካላቸው… የእኛንም የግንቦት 20 ፍሬዎች ይስሙልን (ከእነሱው የተገኘ በረከት ነውና!)
ለህዝባችን ፕሮግራማችንን ለማስተዋወቅ አቅደን፣ ህዝባዊ ስብሰባ እናደርጋለን ብለን ካወጅንበት ዕለት አንስቶ የሚደርስብን ወከባ፣ ድብደባና እስር እንዲሁም የዕቅድ መስተጓጐል …ከግንቦት 20 ፍሬዎቻችን በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡ (እነዚህን ነው ስንኮመኩም የኖርነው!) የተቃውሞ ሰልፎችን በልማት ሰበብ ባሰብነው ቀንና ሥፍራ እንዳናካሂድ በየጊዜው መደናቀፋችንም ሌላው የግንቦት 20 ፍሬያችን ነው፡፡ በየክልሉ በወረዳና በዞን ኃላፊዎች የሚፈፀምብን ድብደባና እስር (ሞባይል መንጠቅን ይጨምራል!)፣ የዲሞክራሲያዊና ሰብኣዊ መብቶች ጥሰት… የግንቦት 20 ፍሬዎቻችን እንደሆኑ ስንገልፅ በታላቅ ሃፍረት ነው፡፡ የኢህአዴግ “ፀረ - ሰላም፣ ፀረ - ልማት፤ ፀረ - ዕድገት፣” ወዘተ… ፍረጃም ለእኛ የግንቦት 20 በረከታችን ነው፡፡
ለዚህ ነው ሁሉም የየራሱን የግንቦት 20 ፍሬዎች እንዲናገር ዕድል ይሰጠው የምንለው፡፡ ለዚህ ነው የኢህአዴግ የግንቦት 20 ፍሬዎች፣ ከኛ የግንቦት 20 ፍሬዎች ይለያሉ የምንለው፡፡ እነ ኢህአዴግ የእኛን የግንቦት 20 ፍሬዎች በግድ እንዲቀበሉን አናስገድድም (“ህልም እንደፈቺው ነው” ብለው ይለፉት)፡፡ እኛንም ግን የእነሱን የግንቦት 20 ፍሬዎች እንድንቀበል አያስገድዱን (የሌሎችን መብት ማክበር ከዚህ ይጀምራል!)
ድል ለሰፊው ህዝብ!!
የግንቦት 20 ፍሬዎች - ለዳያስፖራ ተቃዋሚዎች
ስለ ግንቦት 20 ፍሬዎች መናገር ያለባቸው የወያኔ (ኢህአዴግ ሊሉ ፈልገው ነው!) ሹማምንት እንጂ እኛ አይደለንም፡፡ (የፍሬው ተጠቃሚ እኮ እነሱ ናቸው! እንኳንስ እኛ በርቀት ያለነው የዳያስፖራ ፖለቲከኞች ቀርቶ፣ እዚያው አገር ቤት ያለው ምስኪኑ የኢትዮጵያ ህዝብም ቢሆን  የግንቦት 20 ፍሬዎች ምኑም እንዳልሆኑ መናገሩ አይቀርም (ነፃነት የለም እንጂ!) “የባለሁለት ዲጂት የኢኮኖሚ ዕድገት” ተጠቃሚው ድሃው ህዝብ ሳይሆን የወያኔ (ኢህአዴግ ለማለት ፈልገው ነው!) ባለስልጣናት ናቸው፡፡ ድሃው ህዝብማ አሁንም ድሃ ነው፡፡ ለእሱ የግንቦት 20 ፍሬው የበለጠ ድህነት ሆኗል፡፡
ወያኔ በፈጠረው የኢኮኖሚ ሥርዓት ኑሮው የተመሰቃቀለው የከተሜው ነዋሪ፤ በታክስና በቫት ወገቡ ተቆርጦ መንቀሳቀስ አቅቶታል፡፡ ገበሬው በብድር በወሰደው ማዳበሪያ በእዳ ተቀፍድዶ፣ የፖለቲካ ነፃነቱን ተነጥቋል፡፡ እነዚህ ናቸው እንግዲህ የኢትዮጵያ ህዝብ የግንቦት 20 ፍሬዎች!! ወያኔ ነገ ጠባ የፈረደበትን ኮብልስቶንና የባቡር ሃዲድ እያሳየ፣ አገሪቷን እያለማ እንደሆነ ይደሰኩራል፡፡ (ድንጋይ ዳቦ ይሆናል እንዴ?) ህዝቡ ግን የሚላስ የሚቀመስ አጥቶ ይሰቃያል፡፡ (እንኳን በቀን ሶስቴ አንዴም መብላት ተስኖታል!)
ለእነ ጅቡቲና ሱዳን የኤሌክትሪክ ሃይል እየሸጠ ዶላር ወደ ካዝናው የሚያስገባው የወያኔ መንግስት፤ (የኢህአዴግ መንግስት ለማለት ፈልገው ነው!) ህዝቡን ጨለማ አውርሶት ወደ 16ኛው ክ/ዘመን መልሶታል፡፡ አሁን አሁንማ አራት ኪሎ ቤተመንግስትና የባለስልጣናት መኖርያ ቤት ካልሆነ በቀር መብራትና ውሃ ማግኘት ዘበት ነው እየተባለ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ነዋሪ ለዓመታት በታክሲ እጦትና ወረፋ ከመሰቃየቱ የተነሳ፣ ጋሪና ባጃጅ ቢገቡለት ደስታውን አይችለውም፡፡ (ድንቄም የአፍሪካ መዲና!) የወያኔ ባለስልጣናት ግን በህዝብ ገንዘብ በተገዙ የሚሊዮን ብር አውቶሞቢሎች ይንፈላሰሳሉ። (የግል አውሮፕላን አለመጠየቃቸውም እነሱ ሆነው ነው!) እኒህ ናቸው እንግዲህ የህዝቡ የግንቦት 20 ፍሬዎች!!
ከሁሉም የሚያስገርሙትና የሚያሳዝኑት ደግሞ የወያኔን መንግስት በምርጫ እንጥላለን ብለው አገር ቤት የተቀመጡት አብዛኞቹ ተቃዋሚ ተብዬዎች ናቸው፡፡ (ሰልፍ እንኳ አይፈቀድላቸውም እኮ!) ጥቂቶቹ ተቃዋሚ ተብዬዎች ደግሞ ከወያኔ ፓርቲ ጋር የጋራ ምክር ቤት አቋቁመው፣ የሚጣልላቸውን ድርጐ እየጠበቁ፣ የወያኔ መንግስት የፕሮፓጋንዳ መሳሪያ ሆነዋል፡፡ (ከወያኔ ቅንጣት ሥልጣን የሚገኝ መስሏቸው እኮ ነው!)
ግራም ነፈሰ ቀኝ አገር ቤት ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚታገሉ የቁርጥ ቀን ልጆች (ተቃዋሚ ፓርቲዎች) እንደሌሉ የዳያስፖራ ተቃዋሚዎች የተረዱት ዛሬ አይደለም፡፡ በ97 ምርጫ ማግስት ነው፡፡ ለዚህ እኮ ነው ራሱ የወያኔ መንግስት “ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ ለማግኘት አልታደልኩም” እያለ የሚያፌዝባቸው! የሆኖ ሆኖ ወያኔን በሰላማዊ ትግል መጣል አንድም ቅዠት አሊያም ጅልነት እንደሆነ የዳያስፖራ ተቃዋሚ ያምናል፡፡ ምርጫ ለወያኔ፣ የስልጣን ዕድሜውን ማራዘምያና ለጋሽ አገራትን ማጭበርበርያ መሳሪያ መሆኑ አዲስ ግኝት አይደለም፡፡ እናም የዳያስፖራው ተቃዋሚ በዚህ ፈጽሞ ሊሸወድ አይችልም፡፡
በመጨረሻ የወያኔን የስልጣን አልጠግብ ባይነት ለመግታትና ሥልጣን ለባለቤቱ ለሰፊው ህዝብ እንዲመለስ ለማድረግ፣ የዳያስፖራው ተቃዋሚ የሚከተለውን ባለ 5 ነጥቦች የአቋም መግለጫ አውጥቷል፡፡
የአሜሪካ መንግስት ለወያኔ የሚያደርጋቸውን ማናቸውም የገንዘብ ድጋፎችና እርዳታዎች እንዲያቆም መጠነ-ሰፊ ሎቢ ይደረጋል!
የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ የሚገኘውን ኤምባሲውን ዘግቶ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱን እንዲያቋርጥ ከፍተኛ ግፊትና ጫና እንጀምራለን፡፡
አሜሪካውያንም ሆኑ የዳያስፖራ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ውስጥ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዳያፈሱ መረር ከረር ያለ ቅስቀሳ እናካሂዳለን፡፡
ድል ለኢትዮጵያ ጭቁን ህዝብ!!
የግንቦት 20 ፍሬዎች - ለመንግስት ሚዲያ
ግንቦት 20 ይዞልን ከመጣው ዕልፍ አዕላፍ በረከቶች አንዱና ዋነኛው የፕሬስ ነፃነት መሆኑ አሌ የማይባል ሃቅ ነው፡፡ ዛሬ ዜጐች ያሻቸውንና የመሰላቸውን ሃሳብ ያለምንም ገደብ የመግለጽ ሙሉ ነፃነታቸው ተከብሮላቸዋል - ዕድሜ ለግንቦት 20 ፍሬዎች! የመንግስት ሚዲያዎች ምንም እንኳን ይሄን የግንቦት 20 ፍሬ ተጠቅመው መስራት የሚገባቸውን ያህል በስፋት ሰርተዋል ባይባልም ቢያንስ የህዝብ አጋርነታቸውንና ልማታዊነታቸውን ለማሳየት ተግተዋል ማለት ይቻላል፡፡ በጥፋት ጐራ ከተሰለፈው የግሉ ፕሬስ የሚለያቸውም ይሄው ህዝባዊነታቸውና ልማታዊነታቸው እንደሆነ እሙን ነው፡፡
በቅርቡ የተካሄዱ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት፤ ጨለምተኝነት፣ መርዶ ነጋሪነት፣ ዕድገትን የመካድ አባዜ፣ የፅንፈኛ ተቃዋሚዎች አፈቀላጤነት፣ የኒዮሊበራሊዝም አቀንቃኞችን እንደዘገባ ምንጭ መጠቀም፣ ህገመንግስቱን የመናድ እንቅስቃሴ… ወዘተ የግል ፕሬሱ መለያ ባህርያት ሆነዋል፡፡ በአንፃሩ የመንግስት ሚዲያ፤ ልማታዊ መንግስታችን ያስመዘገባቸውንና እነ IMF ሳይቀሩ ያመኑባቸውን የእድገት እመርታዎች በትክክል በመዘገብ፣ በመላ አገሪቱ ወደርየለሽ መነቃቃትን ፈጥረዋል፡፡ በዚህም የግሉን ፕሬስ የጥፋት ብዕር በልማት ብዕራቸው በመመከት፣ የህዝብና የመንግስት አጋርነታቸውን አሳይተዋል፡፡
የግሉ ፕሬስ፣ በአመፅና ሁከት የአገሪቱን ሰላም ለማደፍረስና ህገመንግስቱን በሃይል ለመናድ የተንቀሳቀሰውን ያህል፣ የመንግስቱ ሚዲያም ሰላምና ልማትን እንዲሁም ህግና ስርዓትን በመስበክ ለህገመንግስቱ ዘብ ቆሟል፡፡ በአጠቃላይ የግሉ ፕሬስ (ከጥቂቶች በቀር) ለአገር ጥፋት፣ የመንግስት ሚዲያ ደግሞ ለአገር ልማት የቆሙ እንደሆኑ ጥናቶች አመልክተዋል፡፡ ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብም ማን የህዝብ አፈቀላጤ፣ ማን ደግሞ የፅንፈኛ ተቃዋሚ ልሳን እንደሆነ በግልፅ ይመሰክራል፡፡
እስከአሁን ድረስ የግሉ ፕሬስ ከጥፋት ተግባሩ እንዲታረም ልማታዊ መንግስታችን ለምን ህጋዊ እርምጃዎችን ሳይወስድ በትዕግስት እንደቆየ በቅጡ እንገነዘባለን፡፡
የግንቦት 20 ፍሬ የሆኑት የግል ፕሬሶች እንዲያብቡ ብሎ ነው፡፡ ነገር ግን ይሄንን የመንግስት ትዕግስት የግሉ ፕሬስ ከፍርሃት በመቁጠሩ፣ ከዕለት ወደ ዕለት እየባሰበት እንጂ እየተሻለው አልመጣም፡፡ ስለዚህም ለህዝብና ለአገር ደህንነት፣ እንዲሁም ግንቦት 20 ያጐናፀፈንን የፕሬስ ነፃነት ለመጠበቅ ሲባል፣ ልማታዊው መንግስታችን ህጋዊ እርምጃዎችን እንዲወስድ እናሳስባለን፡፡ (የፕሬስ ነፃነት እሳት ማንደድ አይደለም!)
በተጨማሪም የአንዳንድ የግል ፕሬሶች የገንዘብ ምንጭ በአግባቡ ተጠንቶ፣ ከጀርባቸው ማን እንዳለ ሊታወቅ ይገባል ብለን እናምናለን፡፡ (አገራችን የቀለም አብዮተኞች ሰለባ እንዳትሆን ለመታደግ!) ጋዜጠኞችና አክቲቪስቶች እዚህና እዚያ ማጣቀሱን ትተው ሚናቸውን መለየት ይኖርባቸዋል፡፡ መፃፍ የቻለ ሁሉ “ጋዜጠኛ ነው” ሊባል ስለማይችል፣ የጋዜጠኝነት መስፈርት የሚያወጣና የብቃት ማረጋገጫ የሚሰጥ ተቋም በአፋጣኝ እንዲቋቋም እናሳስባለን፡፡
በሌላ በኩል፤ ብዙም ወደ ጥፋቱ ጐዳና ያልገቡ የግል ፕሬሶችን በድጎማና በማበረታቻ በመማረክ፣ ወደ ልማታዊ ጋዜጠኝነት የመቀየር ጥረትም ቸል ሊባል እንደማይገባው እናሳስባለን፡፡
ለግንቦት 20 ፍሬዎች - ዘብ እንቆማለን!!!
የግንቦት 20 ፍሬዎች - ለኢህአዴግ ካድሬዎች!
ዛሬ በአገራችን ላይ የምናያቸው መልካም ነገሮች ሁሉ የግንቦት 20 ፍሬዎች መሆናቸውን ራሳቸው ተቃዋሚዎችም ቢሆኑ ሊክዱት አይችሉም፡፡ በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባት፣ ልጄ ለጦርነት ይማገድብኛል ከሚል ስጋት ተላቆ መኖር፣ ንግድ አቋቁሞ ማትረፍ፣ በፈለጉት ሃይማኖት ማመን፣ በብሄር ማንነት ከሚደርስ ጭቆናና አድልኦ ተላቆ በእኩልነት መኖር፤ ወዘተ… የግንቦት 20 ፍሬዎች ናቸው፡፡ ባለፉት አስርት ዓመታት ያስመዘገብነው ተከታታይ ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ ዕድገትም ከግንቦት 20 ፍሬዎቻችን በተቀዳሚነት ተጠቃሽ ነው፡፡
በመላ አገሪቱ ከጫፍ እስከ ጫፍ እየተዘረጋ ያለው መሰረተ ልማትም የግንቦት 20 ፍሬዎቻችን አካል ነው፡፡ ታላቁ የህዳሴ ግድባችንም በፊታውራሪነት የሚሰለፍ የግንቦት 20 በረከታችን ነው፡፡ የገዢውን ፓርቲ መንግስትነት ክደው፣ ነጋ ጠባ በክፉ የሚያብጠለጥሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎችና የእነሱ አፈ ቀላጤ የሆኑት የግል ፕሬሶችም ቢሆኑ… የግንቦት 20 ፍሬዎች ናቸው፡፡ (እነሱ ወፍ ዘራሽ ነን ቢሉም!)
አረረም መረረም እኒህን አያሌ የግንቦት 20 ፍሬዎች ተንከባክቦ ሊጠብቃቸው የሚችለው ከመጀመሪያም መኖራቸውን አምኖ የተቀበለ ወገን ብቻ ነው፡፡ እናም ፅንፈኛ ተቃዋሚዎችና የጥላቻ ፖለቲካ አራማጆች እንዲሁም የእነሱ ልሳን የሆኑት የግል ፕሬሶች፣ የግንቦት 20 ፍሬዎቻችንን (ሰላማችንን፣ ዕድገታችንን፣ ልማታችንን፣ ዲሞክራሲያችንን፣ ወዘተ…) እንዳይንዱብን ከህዝባችን ጋር በመሆን በዓይነ ቁራኛ መጠባበቅ ይኖርብናል፡፡ በተለይ ደግሞ ለህገመንግስታችን ዘብ ልንቆም ይገባል፡፡ ዛሬ የምናጣጥመውን መብትና ነፃነት ለማምጣት ስንት ዘመንና የስንቶችን መስዋዕትነት እንደጠየቀ አንዘነጋውም፡፡ እናም በግንቦት 20 ፍሬዎቻችን ፈፅሞ አንደራደርም (የቀረው ይቀራል እንጂ!)
ድል ለልማታዊ መንግስታችን!!

“ፓርቲ በፍፁም ሊሳሳት አይችልም፤ እኔና አንተ እንጂ!”

አርተር ኮስትለር
ክፍል ሶስት
ውድ አንባቢያን ባለፉት ሁለት ሳምንታት መጣጥፌ እየተማማርና እየተዝናናን ዛሬ ላይ ደረስን፡፡ ለዛሬ እስኪ ይሄን ጀባ ልበላችሁ፡፡ መልካም ንባብ፡፡ እናላችሁ በዚሁ የመረጃ ማሰባሰብ ወቅት ታዲያ በየመንደሩ መዞርና ሱፐርቫይዝ ማድረግ ግድ ነውና ከባልደረባዬ ጋር በእግራችን ስንቀሳቀስ ቆይተን “ይሄነው ነጋ ልኳንዳ ሴንተር” ከሚል ማስታወቂያ ጋር ተፋጠጥን፡፡ ቴሌ ሴንተር፤ ኦዲዮ ቪዲዮ ሴንተር፤ ሄልዝ ሴንተር እንጂ ልኳንዳ ሴንተር የሚል የንግድ ቤት ማስታወቂያ ገጥሞን የማያውቅ በመሆኑ፣ ፈገግ ሳያሰኘኝ አልቀረም፡፡ ስለ ማስታወቂያ ካነሳሁ ዘንዳ አንድ አዝናኝ ገጠመኝ ላጫውታቸሁ፡፡ ሞባይል መሸጫ መስኮት ላይ በኮምፒዩተር የተጻፈ ማስታወቂያ እንዲህ ይላል “ ሙዚቃ ላይ ሜሞሪ እንጭናለን” አሪፍ አይደለች!
ወደ ጨዋታዬ ልመልሳችሁና ከልኳንዳ ሴንተሩ አጥር ስር በምትገኝ ጥላ ቦታ አረፍ ብለን ከባልደረባዬ ጋር ወጋችንን ስንጠርቅ ድንገት ራሱ ላይ እንደ ቄስ የጠመጠመ፤ አጭር፤ አይኑ ጎላ ጎላ ያለና ከብት ሲያርድ እንደነበረ በሚያሳብቅ ሁኔታ መጫሚያው ላይ ደምና ፈርስ እዚህም እዚያም ያረፉበት ሰው ከቤቱ ብቅ አለና፡፡
“ደህና ሰንብታችኋል ወገኖቼ? ምን ልታዘዝ?”
“እግዚአብሄር ይመስገን ፡፡ ለጊዜው ምንም አያስፈልገንም፡፡”
“ግድ የለም ቤት ያፈራውን ቅመሱ፡፡ ኑ ከቤት ግቡ፡፡”
ችኮላው እያሳሰበንና ልግስናው እያስገረመን በመጠራጠር አይን ስንታዘበው፤
“እሺ የሸገር ሰዎች ትመስላላችሁ፡፡ እውነቴን ነው?”
“አዎ፡፡”
“ሸገር የት?”
“መስቀል ፍላወር አካባቢ፡፡”
“ሙሉሸዋ ስጋ ቤት፤ የመንገዶች ባለስልጣን ጋራዥ፤ ድሪም ላይነር ሆቴል፡፡” ሲያከታትል፡፡
አይ ይሄ ሰው ቢያንስ ለንግድ ስራ አዲስ አበባ ይመላለሳል ማለት ነው የሚል የሚል ቅድመ ትንበያ ልናስቀምጥ ስንዘጋጅ፣ አሁንም ፋታ ሳይሰጠን ስለምንሰራው ስራ ዓይነት፤ መቼ እንደመጣን ጠየቀና በረዥሙ እኔን (ጸሀፊውን) አስተዋለና በትግርኛ “አበይ ‘ዩ አድኻ?”
(አገርህ የት ነው?)”
ጨዋታው ቅኔ አዘል መሆኑ ገባኝና “ አድዋ “
“ዋእ! አድዋ እንድህር ኮይንኻ አብ ዘይስራህኻ ታይ ትገብር ?” (አድዋ ከሆንክ ታዲያ ያለ ስራህ እዚህ ምን ታደርጋለህ?”)
ብዙም ማውራት ሳልፈልግ፣ ቅኔው እንደገባኝ የሚያሳብቅ ፈገግታን ብቻ ለግሼው ዝም አልኩ፡፡
“እባካችሁ በሞቴ ግቡና ትንሽ ጥብስ ቢጤ እንቅመስ?”
“አሁን ነው የበላነው እናመሰግናለን፡፡” ጓደኛዬ ተግደረደረች፡፡
“ነይ እንግባ፡፡” ሃሳብ ቀየርኩ፡፡
ታዲያ ይህ ሰው አዲስ አበባ ውስጥ አስከፊ ውጣ ውረድ ያሳለፈና በመልካም አስተዳደር ችግር ምክንያት ለ25 ዓመታት ፍላሚንጎ አካባቢ ይኖርበት የነበረው  ንብረቱ ከህግ ውጪ የተወረሰበት፤ ይህ ቃለ መጠይቅ እስከ ተካሄደበት ጊዜ ድረስ ንግድ ቤቱ አሁንም ታሽጎ የሚገኝ፤ የቀድሞውን ከንቲባ ኩማ ደመቅሳን ለማግኘት ቢሮክራሲው ናላውን አዙሮት ሁሉንም ነገር ትቶ ወደ ሱዳን ሊጠፋ ሲል በቤተሰብ ክትትልና ፍለጋ አእምሮውን ስቶ ጎንደር ላይ ተይዞ አሁን በመጠኑም ቢሆን የተረጋጋ የሚመስል ህይወት በመምራት ላይ የሚገኝ ግለሰብ ነው፡፡ አብሬው ጥቂት ጊዜ አሳልፌያለሁ፡፡ መልካም ቆይታ፡፡
ጠያቂ- “ስምዎን ማን ልበል?”
መላሽ- “ነጋ ተገኝ እባላለሁ፡፡”
ጠያቂ- “ደብረ ታቦር ስጋ ቤት ከፍተው እየነገዱ ነው ያገኘሁዎት እና ስራ እንዴት ነው?”
መላሽ- “ቢቸግር ነው አንተው፡፡ ኽዋናው መንገድ ኑሮ ቢሆን ነው እንጂ ኽዚህ ውሻቆ ውስጥ ማን መጥቶ ይገዛ ብለህ?”
ጠያቂ- “እኔ የምለው ቅድም ስለ አዲስ አበባ በደንብ እንደሚያውቁ በሚያሳብቅ ሁኔታ ነበር ሲናገሩ የነበረውና፤ አዲስ አበባ ኖረዋል እንዴ?”
መላሽ- አዎ፡፡ አዲስ አበባ ከደርግ ጊዜ ጀምሮ ወደ 25 ዓመታት ያህል ኖርያለሁ፡፡ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 (በቀድሞው ቀበሌ 20/21) የቤት ቁጥር 375/ለ ውስጥ ስኖር ነበር፡፡ ኢህአዴግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር “ ሎሚ አይነይ በርኸ (ዛሬ አይኔ በራ) ብዬ የተቀበልኩ እኔ ነበርኩ፡፡ አስተሳሰቤም ኢህአዴግ ነው፡፡ ስሌቴም በኢህአዴግ ቀመር ነው የሚመራ፡፡ ዛሬ እኔ መልምዬ ለቁም ነገር ያደረስኳቸውና ውለታ የሰራሁላቸው ሰዎች ለእኔ ክፉ ሆነው ከጨዋታ ውጭ አድርገውኝ ከድጡ ወደ ማጡ ተወርውሬ እገኛለሁ፡፡ እሱን በደሌን ሳወራ በጣም ይዘገንነኛል፡፡ ስማኝ ወዳጄ እኔ ይሄንን ስርአት የፈለኩበት ምክንያት ከአሰቃቂው የደርግ ስርዓት ጭቆና ነጻ ያወጣኝ በመሆኑ ነው፡፡ አሁንም የደረሰብኝ በደል ተሸክሜ እዚህ ያገኘህኝ ቀድሞ አላማውን ደግፌ አብሬው ስሰራ ከነበርኩት ፓርቲ ጋር ዛሬ በድሎኛል ብዬ ስሙን ሳጠፋ መገኘት የለብኝም፡፡ ሰዎች እንጂ ፓርቲው መች በደለኝ፡፡ ሰው እንዴት በሁለት ቢላዋ ይበላል ብዬ ነው?
ጠያቂ- የደረሰብዎት በደል ምንድን ነው?
መላሽ- ይገርምሃል… ከላይ በጠቀስኩልህ አድራሻ ፍላሚንጎ አካባቢ የሚገኝ የጫት ንግድ የማካሂድበት ሱቅ ነበረኝ፡፡ ንግድ ቤቱ ጥቅምት 2004 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባወጣው የተከራይ አከራይ ህግ ምክንያት አለአግባብ የንግድ ቤቴን ተቀማሁ፡፡ የቀማኝ ማን መሰለህ? የገዛ ጓደኛዬ፡፡ አብሮኝ የሚበላ አብሮኝ የሚጠጣ፣ ህይወቱን አንድ ወቅት ከክፉ ፈተና የታደግሁት፡፡
ጠያቂ- ከክፉ ፈተና የታደግሁት ሲሉ ምን ማለትዎት ነው?
መላሽ- ይህውልህ ልጁ የናዝሬት ልጅ ነው፡፡ መኪና ሃብት ንብረት የነበረው፡፡ ኋላ ላይ ኤች አይ ቪ/ ኤድስ ይዞት ተስፋ ቆርጦ መውደቂያ አጥቶ ሲንከራተት ቤቴ አስገብቼ ተንከባክቤ ጤንነቱን የመለስኩለት ሰው ነበር፡፡ የጫት ንግዱን ስነግድ አብሮ እያገዘኝ፤ እኔ በሌለሁ ጊዜ ስራውን እየሸፈነ ሲሰራ የነበረ ሰው ነው ዛሬ ይህን በደል የፈጸመብኝ፡፡
ጠያቂ- የፈጸመው በደል ምን ነበር?
መላሽ- ይሄውልህ ወንድሜ፡፡ ንግድ ቤቱ የንግድ ፍቃዱ በእኔ ስም ነው፡፡ የንግድ ቤት ኪራይ የሚከፈለው በእኔ ስም ነው፡፡ እኔ በሌለሁበት ንግዱን እንዲያካሂድ የሰጠሁት ምንም አይነት ውክልና በሌለበት ባጋጣሚ እናቴን መጠየቅ ስለነበረብኝ ቤቱን እየጠበቀ ስራውን እንዲያካሂድ ሀላፊነት ሰጥቼው ወደ ሀገር ቤት ሄድኩኝ፡፡
ጠያቂ- ከዚያስ?
መላሽ- ከዚያማ እኔ ገጠር በነበርኩበት አጋጣሚ፣ ጥቅምት 2004 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቀበሌ ቤቶችን ለሌላ ወገን ያከራዩ ግለሰቦች ንግድ ቤታቸው እንዲወረስ የሚል የተከራይ አከራይ ህግ አወጣ፡፡ ይህን ተከትሎ ሱቁን እንዲጠብቅ ሀላፊነት የሰጠሁት ግለሰብ ስልኬ ላይ ይደውልና “ቀበሌዎች ቤቱን እንወርሳለን እያሉ ስለሆነ ምን ላድርግ”? ይለኛል፡፡
እኔም፤ “የእኔ ሱቅ እኮ ይሄ አዋጅ አይመለከተውም፡፡ ይህን አስረዳቸው፡፡ እምቢ ካሉህ ግን ሱቁን ዝጋውና እኔ ስመጣ አነጋግራቸዋለሁ፤ ግፋ ቢል ንግዱ ቢስተጓጎልብኝ ነው” ብዬ ስልኩን ዘጋሁ፡፡
 ይህ ልጅ ለካ ከሰዎች ጋር ተመሳጥሮና ተማክሮ ሶስት ምስክሮችን አስመስክሮና በወቅቱ ለነበሩት ሀላፊ ጉቦ ሰጥቶ “ተከራይ ነኝ” በማለት “ወራሽ ነኝ” ብሎ ቁጭ አለ፡፡
ጠያቂ- በእርስዎ በኩል ምን አደረጉ ታዲያ?
መላሽ- የቀበሌውን ምልልስ ተወውና አዲስ አበባ መስተዳድር ከ15 ቀናት በላይ ተመላለስኩ፡፡ ፍትህ አጣሁ፡፡ ከዚያልህ ልክ በ11ኛ ወሬ ሁሉም ነገር ተስፋ ሲያስቆርጠኝ  ጨርቄን ማቄን ሳልል ቤተሰቤን ጥዬ በመተማ በኩል ወደ ሱዳን ለመጥፋት ጉዞ ጀመርኩ፡፡ እስከ ባህር ዳር ድረስ ህሊናዬን አውቅ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ጎንደር ላይ ሞባይሌን ጥዬ፤ ቦርሳዬን ተሰርቄ ስንገላወድ እኔን የሚያውቁኝ ዘመዶች ለባለቤቴ ነግረዋት፣ ከአዲስ አበባ ስትበር መጥታ ደረሰችብኝና አረዳድተው፤ አረዳድተው ተረጋጋሁ፡፡
ጠያቂ- ቤተሰቦችዎ ከእርስዎ ጋር አብረው አዲስ አበባ ይኖሩ ነበር?
መላሽ- ታዲያስ!! እዚያው ንግድ ቤቱ ያለበት ግቢ ውስጥ መኖሪያ ቤት ነበረኝ፡፡ ይሄ ልጅም እዚያው ነው የተወለደው፡፡
ጠያቂ- እኔ እስከማውቀው ግን አንድ ንግድ ቤት ብቻ የተወረሰባቸውና ሌላ ገቢ ምንጭ የሌላቸው ሰዎች የተወረሰው ንግድ ቤት እንዲመለስላቸው ተደርጓል፡፡ ይህን እርስዎ ማድረግ አልቻሉም?
መላሽ- ስማኝ ልንገርህ ቀበሌ ምላሽ ሳጣ፣ የወቅቱ ከንቲባ ኩማ ደመቅሳ ብቻ ናቸው ጉዳዩን የሚፈቱልኝ ብዬ ቀጠሮ አስይዤ ስሄድ፣ በር ላይ ያሉ ዘበኞች መታወቂያዬን ተቀብለው ደብድበው አባረሩኝ፡፡
ጠያቂ- የማዘጋጃ ቤት ዘበኞች!?
መላሽ- አዎ፡፡
ጠያቂ- አካሄድዎትን በቅርበት የሚከታተሉ ሰዎች ነበሩ ማለት ነው?
መላሽ- ቴዎድሮስ ታደሰ የሚባልና አባቱ ጓደኛዬ የሆነ ፤ በአካባቢው የታወቀ ነውጠኛ፤ ዱርዬ ልጅ… ከነበረበት ህይወት መክሬና ዘክሬ በማውጣት… ወጣት ሊግ ውስጥ ያስገባሁት ልጅ ነው ይሄን ሁሉ በደል ያደረሰብኝ፡፡
ጠያቂ- ይህን ሁሉ ውለታ ፈጽመውለት እንዴት እንዲህ ሊያደርግ ቻለ?
መላሽ- ውለታ ቢሉህ እንዲህ መሰለህ እንዴ? ደምበል ሲቲ ሴንተር አካባቢ በእናቱ ስም ተመዝግቦ የሚገኝ የቀበሌ ቤት ለልማት በሚነሳበት ወቅት በእናቱ ስም ሲኤምሲ ኮንዶሚንየም ቤት እንዲያገኝ ካደረኩ በኋላ፣ በእኔ ስም ደግሞ ሌላ ቤት ማግኘት አለብኝ የሚል ጥያቄ አቀረበ፡፡ እኔም ጉዳዩ ፍትሃዊ ስላልሆነ አይገባህም አልኩኝ፡፡ በዚህ መሀል ሌሎች የኮሚቴውን አባሎች አሳምኖ ቀረበና “እነርሱ ፍቃደኛ ናቸው፤ አንተ ለምን ትከለክለኛለህ?” ብሎ የሙጥኝ አለ፡፡ ምንም እንኳን ባላምንበትም በእኔ ምክንያት ቤት ከሚያጣ በማለት፣ በዚያው የቤት ቁጥር ስሙን አስተላልፈን፣ ጎፋ ካምፕ ባለ ሁለት መኝታ ቤት ኮንዶሚንየም እንዲያገኝ ተደረገ፡፡ ነገር ግን ልጁ በዚያን ጊዜ ቂም ሳይቋጥር አይቀርም ነበርና ጊዜ ጠብቆ ሊበቀለኝ ሞከረ፡፡
ጠያቂ- እርስዎ በወቅቱ አመራር ነበሩ?
መላሽ- ኢህአዴግ ከገባ ጀምሮ በአመራርነት፤ በልማት ኮሚቴ ሰብሳቢነት፤ የቀበሌ 06 መዝናኛ ማእከልን ከዜሮ አንስቼ እስከ 200 ሺህ ብር ካፒታል ያደረስኩ ነበርኩ፤ ምን ዋጋ አለው እኔማ ለተጨቆኑ የሚቆም መንግስት የመጣ መስሎኝ ነበር፤ ለካም “አማርኛ የሚናገረው ደርግ ሂዶ ትግርኛ የሚናገረው ደርግ ነው የተተካው፡፡”
ጠያቂ- ይሄን ያህል ተማረዋል ማለት ነው?
መላሽ- እንዲህ ናትና!! እኔ ለልማት ስታገል ምን ያልደረሰብኝ አለ መሰለህ? በ1997 ዓ.ም ምርጫ ወቅት ከመሬት ተነስተው “የቅንጅት ደጋፊ ነህ አሉኝ፡፡”እንገማገም” ብዬ ነጻ ወጣሁ፡፡ በ2002 ዓ.ም ምርጫ የተከበሩ አቶ አለማየሁ ተገኑን ለማስመረጥ የእኔ ሚና ከፍተኛ ነበር፡፡ ባይገርምህ ይህ ሁሉ በደል ተፈጽሞብኝ፣ እዚህ ደብረ ታቦር መጥቼ እንኳን ከእኔ ቤት በታች ለሚኖሩ 11 አባወራዎች በግል ገንዘቤ መጸዳጃ ቤት አሰርቼ አስረክቤያለሁ፡፡ ይህ ስራዬም በከተማው ኤፍኤም ቀርቦ ተመስግኛለሁ፡፡ አንድ ጊዜ ትግል ብለህ ከገባህ እኮ ብትበደልም ላመንክበት አላማ መኖርህ መቋረጥ የለበትም፡፡
ጠያቂ- አቶ ነጋ እኔ ወደ አዲስ አበባ ስመለስ ይህን በደል በምችለው አቅም በሚዲያ እንዲወጣ ለማድረግ እሞክራለሁ፡፡
መላሽ- አታወጣውም አንተው! እንዲያው ወጉን ላውጋችሁ ብዬ እንጂ አንተስ አታወጣውም ተወው፡፡
ጠያቂ- ይመኑኝ የምችለውን አድርጌ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሰሙት አደርጋለሁ፡፡
ይድረስ ሀገር ለምትመሩ የኢህአዴግ ባለስልጣናት!
እውነት የአፍሪካ መዲና እና የፌደራል መንግስቱ መቀመጫ በሆነች አዲስ አበባ አፍንጫ ስር እንዲህ አይነት አስከፊ የመልካም አስተዳደር በደል እየተፈጸመ ልማትን ማረጋገጥ ይቻል ይሆን? የአባላትን ቁጥር በብዛት ብቻ ሳይሆን በጥራት ማፍራት እንደሚያስፈልግ፤ ከዚያም ባለፈ ወደ አመራር የሚመጡ አባላት ከግል ጥቅማቸው ይልቅ የህዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚችሉ ካልሆኑ፣ መንግስት ብሎም ሀገር እየመራ ያለው ኢህአዴግ ከተጠያቂነት መቼም ቢሆን አይድኑም፡፡
Arther Koestler, Darkness at noon በተባለው መጽሀፉ “The Party can never be mistaken…You and I can make the mistake. Not the Party.” (ፓርቲ በፍጹም ሊሳሳት አይችልም… እኔና አንተ እንጂ፡፡ ፓርቲማ በፍጹም!) ማለቱን ልብ አድርጉልኝማ!

Page 4 of 21