ሰውየው ወደ አደን ሊወጣ እየተዘገጃጀ ነው፡፡ መሣሪያ ሲያዘጋጅ፣ ጥይት ሲቆጥር ጥሩሩን (የውጊያ ልብሱን) ሲያጠልቅ፤ ዝናሩን ሲታጠቅ፤ ከአፋፍ ሆኖ የሚያስተውለው ጎረቤቱ፤ “ምን ጉድ መጣ? መጠየቅ አለብኝ ብሎ ወደ ቁልቁል ወረደ፡፡
ታጣቂው ሲወጣ ጎረቤቱ አገኘው፡፡
“እንዴት አደርክ ወዳጄ!” አለ አዳኙ ሞቅ አድርጎ፡፡
“ደህና እግዚሃር ይመስገን! አንተስ እንዴት አድረሃል?”
“ወደ ደጋ ወጥቼ ሠርጉም፣ ልቅሶውም ተደባልቆብኝ፤ እሱን ተወጥቼ መምጣቴ ነው! አሁንኮ ካፋፍ ላይ ሆኜ ቁልቁል ሳስተውል ትጥቅህን ስታዘጋጅ አይቼህ ምን ገጥሞት ይሆን? ብዬ ነው ልጠይቅህ የመጣሁት?” አለው፡፡
“የለም፤ ወደ ጫካ ለአደን እየሄድኩ ነው፡፡”
“ምን ልታድን አስበህ ነው?”
“ነብር”
“ነብር?!” አለ ጎረቤት፤ በድንጋጤ፡፡
“ምነው ደነገጥክ?”
“ነብር አደገኛ ነዋ!”
“ቢሆንም ተዘጋጅቻለሁ፤ አሳድጄ እገድለዋለሁ!”
“ብትስተውኮ አለቀልህ ማለት ነው፡፡ እሺ ብትስተው ምን ይውጥሃል?”
“ከሳትኩማ ወዲያውኑ አቀባብዬ ደግሜ እተኩሳለሁ”
“ሁለተኛ ጊዜ ብትስተውስ?”
“ወዲያው ለሶስተኛ ጊዜ አቀባብዬ ግንባሩን እለዋለሁ!”
“ለሶስተኛ ጊዜ ብትስተውስ?”
“እህ! አንተ ከእኔ ነህ ወይስ ከነብሩ?!”
*      *      *
ነገርን ከአሉታዊ ገፁ አንፃር ብቻ ማየት እጅግ ጎጂ ባህል ነው! ለሀገር ዕድገት ስንል፡፡ ለሀሳብ ነፃነት ስንል፤ በምንደክምበት ረዥም መንገድ ከማን ጋር መጓዝ ተገቢ እንደሆነ ያልለየ ጋዜጠኛ ዓላማና ግቡ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ነው፡፡ ቢያንስ የቱ ድረስ ተራራውን አብረን እንጓዛለን ማለት ያባት ነው! የሀገር ጉዳይ ከፅሁፍና ከሀሳብ ነፃነት ተለይቶ አይታይም - ዲሞክራሲያዊ አካሄድ አለን የምንል ከሆነ፡፡ የህዝቡን መረጃ የማግኘት ነፃነት ሳናከብር ለሀገርና ለህዝብ ዲሞክራሲያዊ መብቶች እየታገልን ነው ብንል ቢያንስ ወይ ለበጣ ወይ የዋህነት ነው፡፡ ሳይማሩ ማስተማር ለአስተማሪውም ለተማሪውም ኪሳራ አለው፡፡ አመለካከትን ያዛባል፡፡ ጎዶሎ ዕውቀት ሊሆን ይችላል፡፡ የአላዋቂነትን ገደል ያሰፋል፡፡ ውጤቱም-ያልነቃ፣ የማይጠይቅ፣ ለለውጥ ያልተዘጋጀ ህዝብ ይዞ መኖር ይሆናል፡፡ ያ ደግሞ “ባለህበት ሃይ” ወይም “ቀይ ኋላ ዙር” የሚል የሰልፍ ህግ ከማክበር ያለፈ አገራዊ ፋይዳ የለውም፡፡ አርቀን እናስተውል፡፡ የዓለም ኢንፎርሜሽን ቀን፣ የዓለም ላብ አደሮች ቀን፣ የዓለም የሴቶች ቀን፣ የዓለም የጤና ቀን፣ የዓለም የእናቶች ቀን፣ የዓለም የህፃናት ቀን .. ዛሬም የዓለም የፕሬስ ቀን፤ እናከብራለን እንላለን፤ ሁሉም፤ ሀሳብን በነፃ ጋር ቅርብ ቁርኝት ያላቸው የራቁ ፅንሰ-ሀሳቦች ናቸው፡፡
እዚህ ላይ የፈረንሳይ ፈላስፋ ፒየር ጆሴፍ ፕሩዶንን ማስታወስ ተገቢ ሳይሆን አይቀርም፡- ብዙ ፈላስፎች ህዝብን ለመግዛት በሚፅፉበት ዘመን እሱ ህዝብ ሆነን ስለመገዛት ፅፏል፡- “መገዛት ማለት መታሰብ ማለት ነው፡፡ መታወስ ማለት ነው፡፡ መመዝገብ ማለት ነው፡፡ የመንግስት ቁጥጥር ውስጥ መግባት ማለት ነው፡፡ ተጠያቂ መሆን ማለት ነው፡፡ መለካት ማለት ነው፡፡ ተለይቶ መታየት ማለት ነው፡፡ በኦዲተር መታወቅ ማለት ነው፡፡ የፈጠራ መለያ ማግኘት ማለት ነው፡፡ የንግድ ፈቃድ ማግኘት ነው፡፡ ሥልጣን ማግኘት ነው፡፡ መካተት ነው፡፡ መቀጣት ነው፡፡ መታነፅ ነው፡፡ የእርማት መንገድ ላይ መቀመጥ ነው፡፡ መስተካከል ነው፡፡ ይህ ሁሉ እንግዲህ በየአንዳንዱ ክንዋኔ፣ በየአንዳንዱ ሽያጭና ግዢ እንዲሁም፣ በየአንዳንዱ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚታይ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ መብትን መገፈፍ፣ የመናገር፣ የመፃፍ፣ የመሰብሰብ፣ የመደራጀትን ነፃነት ማጣት፣ አግባብ አይደለም፡፡ ዕውቅና ማጣት መገደብ፣ መገፋት፣ መጣል፣ መረጋገጥ፣ መወገር፣ ወዘተ በኃይል መገዛት ነው፡፡ ያ ደግሞ የዲሞክራሲን ሰፈር አያቅም፡፡
ተገዢዎች ጥበብ እንዳላቸው አንርሳ፡፡ ልምድ እንዳላቸው አንርሳ፡፡ ከትላንት ሊማሩ እንደሚችሉ አንርሳ፡፡ ህዝቦች፤ መማረር፣ መናደድ፣ ማዘን፣ ትተው፤ ዝም ሊሉ እንደሚችሉ አንርሳ፡፡ ዲሞክራሲ ሙልጭ እሚወጣው (Zero Sum) ይሄኔ ነው!
በንፁህ ልቦና የማይሰራ የፕሬስ ሰው ህዝብንም፣ ሙያውንም፣ እራሱንም ይጎዳል፡፡
የፕሬስ ሰው በመደለል አያምንም፡፡ ሥልጣንንም አይቋምጥም፡፡ የኢኮኖሚንም ሆነ የፖለቲካ ሥልጣን ሙሰኞች፤ ስለሐቀኛ ጋዜጠኛ ሲያስቡ የሚጨንቃቸው ለዚህ ነው!
“ተመስጌን ነው!
የእንግሊዝን ጋዜጠኛ
ጉቦ መስጫ፣ ማማለያ
ወይም እጁን መጠምዘዢያ
ቅንጣት ታህል ቦታ የለም!!
ያለጉቦ መስራቱንም
መመልከቻም፣ ጊዜ የለም
መገንዘቢያም፣ ወቅት አደለም!!
ተመስጌን ነው!”
    ይለናል ሐምበር ዎልፍ፤ ጣሊያን የተወለደው እንግሊዛዊ ገጣሚ፡፡
ፕሬስ አጋዤ ነው ብሎ የሚያምን መንግሥት ራሱን ማያ መስተዋት ያገኛል፡፡ ሆደ-ሰፊ አመለካከት፤ አዎንታዊና ገንቢ ምዛኔ ያለው ሥርዓት ጤናማ አገርን ያለመልማል፡፡
“በፕሬስ አትናደድ፡፡ አለበለዚያ አብዛኛው ሥራህ የህዝቡን የፖለቲካ ህይወት ካልገዛሁ ማለት ብቻ ይሆናል፡፡” (ክሪስታቤል ፓንክረስት) ያ ደግሞ የሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ጉዞን ያጨናግፋል፡፡ ጠብታዎችን በሙሉና በጥልቅ ዐይን ማየትና በጊዜ ቦታ ቦታ ማስያዝስ ከብዙ መጪ ጠንቀኛ ዥረቶች ይገላግለናል፡፡
ታሪክ ፀሀፊዎች፤ “በትክክለኛው የታሪክ ወገን መቆም፤ ከዛሬ ጎን ሳይቆሙ ሊደረግ ይችላልን?” በሚለው ጥያቄ ዙሪያ ብርቱ ሙግት ያቀርባሉ፡፡ ነፃ ጋዜጠኛ ግን ይህን ጥያቄ በአዎንታ አይመልሰውም፡፡ ይልቁንም፤ ተጨባጩ ዕውነት ባለበት ቦታ ሁሉ ጋዜጠኛ አለ፤ ይላል፡፡ ምነው ቢሉ፤ የአሜሪካው ፀሐፊና ጋዜጠኛ ሐንተር ቶምፕሰን ነገሩን እንዲህ ይደመድምልናል፡-
“እኔ በአለፉት አሥር ዓመታት የማውቀውን ዕውነት ሁሉ ብፅፍ ኖሮ እኔን ጨምሮ ከሪዮ እስከ ሲያትል ያለው 600 ያህል ህዝብ እስር ቤት ይበሰብስ ነበር፡፡ በጋዜጠኛነት ሙያ ውስጥ፤ ፍፁም ውድና የማይገኝ (rare) እንዲሁም አደገኛ ሸቀጥ (dangerous commodity) ፍፁም እውነት ነው፡፡” ይህ ማለት ግን አንፃራዊ እውነት፣ ተጨባጭ ሁኔታ ላይ የተመረኮዘ መረጃ የለም ማለት አይደለም፡፡ ከላይ ያልነውን ሁሉ ብለን ስናበቃ፤ ስለ ፕሬስና ፕሬስ ሰዎች ለመናገር፣ ከሌላ ዓላማና ግብ አኳያ የተዛባ፣ የተዛነፈ ወይም ፍፁም በሥሃ የተሞላ አመለካከት ይዞ መገኘት፤ “እቺ ጎንበስ ጎንበስ ሣር ፍለጋ ሳትሆን ዱባ ለመስረቅ ናት” ከማለት በቀር ምን ይባላል?!

Published in ርዕሰ አንቀፅ

የአለማቀፉ የፕሬስ ነፃነት ቀን በዛሬው እለት “Media freedom for abetter feauture` በሚል መሪ ቃል ይከበራል፡፡ ይህን ምክንያት በማድረግ በኢትዮጵያ የፕሬስ ካውንስል ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ተሣታፊ ከሆነችው ጋዜጠኛ ሚሚ ስብሃቱ ጋር ጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው እና አለማየሁ አንበሴ ስለሀገራችን የፕሬስ ተግዳሮች ስለ ካውንስል ምስረታው እና የተለያዩ ጉዳዮች ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡  

የአገራችን የፕሬስ ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው ትያለሽ?
እንደ ኢንዱስትሪ ተግዳሮቶቹ ሁለት ናቸው፡፡ ውስጣዊም ውጫዊም ናቸው፡፡ የመገናኛ ብዙሃን ኢንዱስትሪው ራሱን በራሱ የሚቆጣጠርበትና ራሱን በራሱ የሚያሻሽልበት ስርዓት እስከ አሁን ድረስ መገንባት አለመቻሉ ከፍተኛ የማንነት ቀውስ ውስጥ መሆኑን ያሳያል፡፡ ብዙዎችን ለማስተናገድ፣ ብዙ የሰው ሃይል አቅፎ ለመንቀሳቀስ፤ እንደሀገሪቱ ግዙፍነት፣ እንደ ህዝባችን ብዛት የተደራሽነት አቅም እንዲኖር የማያስችል ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ሀገሪቱ ጥርት ያለ የሚዲያ ፖሊሲ የላትም፡፡ በሌሎች አገሮች መገናኛ ብዙሃን እንዲያብቡ፣ እንዲጐለብቱ ብዙ ድጋፍ ይደረጋል፡፡ ማተሚያ ቤቶች እንዲያቋቁሙ ሃሳብ ከመስጠት ጀምሮ በፓርላማ አማካኝነት ከመንግስት ገንዘብ የሚመደብበት አሰራር አለ፡፡ ለምሳሌ በአገራችን የማተሚያ ቤት ችግር አለ፡፡ የእሁዱን ጋዜጣ ረቡዕ እያነበብን ነው፡፡ እነዚህ ሁኔታዎችን ነው እንደ ተግዳሮት የምናስባቸው፡፡
ከ10 ዓመት በፊት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር አሁን ያለው የፕሬስ ደረጃ ምን ይመስላል፡፡ ያኔ በመቶዎች የሚቆጠሩ ጋዜጦች ይታተሙ ነበር፡፡ አሁን በጣት የሚቆጠሩ ናቸው ያሉት….
ከአስር ዓመት በፊት የነበረው የህትመት መገናኛ ብዙሃን ብዛት እንጂ ጥራት አልነበረውም፡፡ መፃፍ የቻለው ሁሉ የፈለገውን የሚጽፍበት ጊዜ ነበር፡፡ ከብሔር ብሔረሰቦች ጀምሮ ግለሰቦች የሚብጠለጠሉበት፤ አንድ ገፅ እንኳን ትክክለኛ ዜናና መረጃ ተፈልጐ የማይገኝበት የህትመት መገናኛ ብዙሃን ነበር፡፡ መገናኛ ብዙሃን ህዝብን መለወጥ አለባቸው፡፡ የህዝብን ህይወት ለማሻሻል ትልቅ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ የሰው ልጅ የመገናኛ ብዙሀንን  የፈጠረው ለሰዎች የተሻለ ህይወት ለማምጣት ነው፡፡
ከዚህ አንፃር ሲታይ ከ10 ዓመት በፊት የነበሩት ምንም ዓይነት ዓላማ ያልነበራቸው፣ እንደውም ህብረተሰቡን ብዥታ ውስጥ የሚከቱ፣ ምንም ዓይነት መረጃ የማይሰጡ፣ በአሉባልታና በወሬ የተሞሉ ነበሩ፡፡ ከአስር ዓመት ወዲህ ያሉት ቁጥራቸው ቢያንስም የጋዜጠኝነት ሙያን እየተገበሩ ነው እስከዛሬ የዘለቁት፡፡ በእርግጥ ከ10 ዓመት በፊት የነበረው ጊዜ የመገናኛ ብዙሃን እድገት አንድ ምዕራፍ ነው፡
ያንን አልፈን አሁን ሁለተኛው ምዕራፍ ላይ ነን፡፡ የመገናኛ ብዙሃን መርሆቻቸውንና ስነምግባሮቻቸውን አክብረው የሚንቀሳቀሱበት፤ መፃፍ የቻለ ሁሉ የፈለገውን የሚዘባርቅበት ሳይሆን ሙያተኞች ወደ ዘርፉ ገብተው የህዝብ ልሳንነታቸውንና አገልጋይነታቸውን በተግባር እያሳዩ ያሉበት ወቅት ነው፡፡ በአገራችን ያለውን የህትመት መገናኛ ብዙሃን ስንመለከት  ምንም የለም ለማለት ያስደፍራል፡፡ የኤሌክትሮኒክስ የመገናኛ ብዙሃን በተወሰነ ደረጃ አድጓል፡፡ በህትመት የመገናኛ ብዙሃን ከብዛት ይልቅ ጥራቱ የሚታይበት ደረጃ ላይ ነው ያለው፡፡
የፕሬስ ካውንስል ለማቋቋም እንቅስቃሴ ስታደርጉ ነበር፡፡  ምን ላይ ደረሰ?
ጨርሰናል ማለት ይቻላል፡፡ በተቋሙና በሥነምግባር ደንቡ (በኮድ ኦፍ ኮንዳክቱ) ላይ የመጀመሪያ ዙር ውይይት አድርገናል፡፡ በቀጣይ ያለውን ሂደት ለመጀመር እየተዘጋጀን ነው፡፡ በቅርቡ አዲስ ነገር ይኖራል፡፡
የአለም የፕሬስ ነፃነት በሚከበርበት ዋዜማ 6 ጦማሪዎች (ብሎገሮች) እና 3 ጋዜጠኞች ታስረዋል፡፡ ዓለማቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቾች ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን በማሰር ከኤርትራ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ እንደምትገኝ ሪፖርት አውጥተዋል፡፡ በእዚህ ጉዳይ ላይ የአንቺ አስተያየት ምንድነው?
በመሠረቱ የጋዜጠኞች  መብት ተሟጋች ነን ብለው የሚንቀሳቀሱ ዓለምአቀፍ ተቋማት ላይ እምነት የለኝም፡፡ ተዓማኒነታቸው የወደቀ ነው፡፡ የሚሠሯቸውን ስራዎች ስለማውቅ ነው፡፡ የሀገራችን ሁኔታም አልጋ በአልጋ አይደለም፡፡ ታሰሩ ስለተባሉት ሰዎች ጉዳይ ፖሊስን ጠይቀን አጣርተናል፡፡ “ከውጭ ሃይሎች ጋር እየተገናኙ በሀገሪቱ ሁከትና ብጥብጥ ለመቀስቀስ ሙከራ ሲያደርጉ ደርሸባቸዋለሁ” ነው ያለው ፖሊስ፡፡
በእርግጥ ጋዜጠኛ አይታሰርም፤ ነገር ግን ጋዜጠኛ አይታሰርም ሲባል ከህግ በላይ ነው ማለት አይደለም፡፡ ህግ መከበር አለበት፡፡ በተለይ ደግሞ አገርን አደጋ ላይ ሊጥሉ ከሚችሉ ነገሮች ከማንም በላይ ቀድሞ ዘብ መቆም ያለበት ጋዜጠኛው ነው፡፡ በዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን የተለመዱት ጩኸቶች ይኖራሉ፡፡ የዘንድሮው የሚከበረው በጣሊያን ነው፡፡ በዛ ቦታ ያ ሩጫ ሊኖር ይችላል፡፡ ግን መታወቅ ያለበት ማንም ቢሆን ጋዜጠኛም፣ ተራ ዜጋም፣ መንግስትም ቢሆን  ከህግ በላይ አይደሉም፡፡ ነፃነት ከሃላፊነት ጋር ነው የሚመጣው፡፡
የሚፃፈው ነገር ምን ያስከትላል ተብሎ መታየት አለበት፡፡ ይሄ የሙያው መርህና ስነምግባር የሚያጐናፅፈው ክህሎት ነው፡፡ በእርግጥ ይህ ሁኔታ መፈጠሩ (ሰዎቹ መታሰራቸው) ደስ የማይልበት ሁኔታ አለ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የማናውቀው ነገር አለ፡፡ ፖሊስ አለኝ የሚለውን ማስረጃና የፍርድ ቤትን ውሳኔ ማየት አለብን፡፡
በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የፀረ ሽብር ህጉ ጋዜጠኞች በነፃነት እንዳይሰሩ እንቅፋት እንደሆነና ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን እየሸረሸረ ነው የሚል ወቀሳ እየተሰነዘረ ነው፡፡ በዚህ ላይስ ምን ትያለሽ?
ሽብር ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን መላው ዓለም  እየተጋፈጠው ያለ አደጋ ነው፡፡ ብዙ ሃገሮች የፀረ ሽብር ህግ አላቸው፡፡ የፀረ ሽብር ህጉ የተለየ ሆኖ ትኩረት የሚስበው የተወሰኑ ሲቪል መብቶችን ስለሚገድብ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለደህንነት የሚከፈል መስዋዕትነት ነው፡፡ በሰላም ወጥቶ ለመግባት፣ በሰላም ልጆችን ለማሳደግ ህዝቦች እንደዚህ አይነቱን ህግ የሚቀበሉበት ሁኔታ አለ፡፡ የመከላከል ህግ እኮ ነው! የጭቃ ሹም አስተሳሰብ ያለው ሹመኛ ያለአግባብ ሊጠቀምበት ይችላል፤ በተገቢው መንገድ ተግባራዊ ከተደረገ ግን አሸባሪዎች ፍንዳታ ከማድረሳቸው በፊት ይያዛሉ፡፡ አወዛጋቢ የሆነው የፀረ ሽብር ህግ፣ በተለያዩ ሀገሮችም አለ፡፡ በተወሰነ ደረጃ በህገመንግስቱ ውስጥ አይነኬ የሆኑት ሁሉ ይነካሉ፡፡ ይሄ ደግሞ ለመዳን ስንል የምናደርገው፤ የምንወስደው እርምጃ ነው፡፡ እኛም እንደባለሙያ መሳሪያ እንዳንሆን መጠንቀቅ አለብን፡፡ የምናገኛቸውን መረጃዎች ደግመን ደጋግመን ማረጋገጥ አለብን፡፡ መረጃ ስለተገኘ ብቻ አይደለም የምንጠቀመው፡፡ የፀረ ሽብር ህጉ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ላይ ጫና ይፈጥራል ብዬ አላምንም፡፡ ሃሳባችንን መግለጽ፣ ጉዳያችንን ማስተጋባት እንችላለን፡፡ እንፅፋለን እናነባለን፡፡ ከህጉ ጋር የምንጋጨው፣ ነፃ አውጭነት ወይም ፋኖነት ሲሰማን ነው፡፡ የእኛ ብዕር ዓላማ ደግሞ ፋኖነት አይደለም፡፡ ተነስ፣ ውጣ ታገል፣ ታሰር… ማለት የእኛ ስራ አይደለም፡፡ ይሄንን ሚዛናዊ አድርጐ የመሄድ ጥያቄ ነው፡፡ የፀረ ሽብር ህጉ የት ላይ ነው ቀጫጭን መስመሮች ያሉት የሚለውን እኛ ማወቅ አለብን፡፡
የመንግስት የመረጃ ስስት የፕሬሱን ዕድገት አቀጭጮታል የሚሉ ሃሳቦች ይሰነዘራሉ፡፡ በዚህ ሃሳብ ትስማሚያለሽ?
መረጃ የማግኘት መብትን በተመለከተ በህግ ተቀምጧል፡፡ ብዙ አገሮች እንደውም የላቸውም፡፡ ኢትዮጵያ የመረጃ ነፃነት ህግ  አላት፡፡ ማህበረሰባችን የመጣበት ሁኔታ በራሱ መረጃ መስጠትን አያበረታታም፡፡ መረጃ መስጠት ግዴታቸው፣ ሃላፊነታቸው መሆኑን የማያውቁ የመንግስት ባለሥልጣናት አሉ፡፡ እንደማህበረሰብ ግልጽ አይደለንም፤ በጣም ዝግ ማህበረሰብ ነው፡፡ ያንን ዝግ ማህበረሰብ ነው ለመክፈትና መረጃ ለማግኘት የምንሞክረው፡፡ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መደበኛ ስራቸው የምርመራ ጋዜጠኝነት (Investigative Journalism) የምንለው ነው፡፡ ምክንያቱም መረጃ ለማግኘት ብዙ ርቀት መሄድ ያስፈልጋል፡፡
የመገናኛ ብዙሃኑ አበቃቀልና አስተዳደግ ታሪክም ለዚህ የሚያመች አይደለም ይፈራል፡፡ መረጃ ሰጪው አካልና ጋዜጠኛው እንደ አጋር ነው መተያየት ያለባቸው፡፡ የምንሰራበት ማዕቀፍ ግን መረጃ መጠየቅና መስጠትን እንደ አይጥና ድመት የሚታይበት ነው፡፡ የህግ ማዕቀፉ ግን ተቀምጧል፡፡ ማንም የመንግስት ባለስልጣን መረጃ የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡
በመገናኛ ብዙሃን አሰራር የዳበረ ባህልና ልምድ ባላቸው አገሮች፣ ምንም ቢፃፍ ማንም ዞር ብሎ አያያቸውም፡፡ ህብረተሰቡ የፀሐፊው እብደት ነው ብሎ ነው የሚያስበው፡፡ የመገናኛ ብዙሃንን እንደ ተፅዕኖ ፈጣሪ (ኦቶሪቲ) የሚወስድ እንደኛ ያለ ማህበረሰብ ውስጥ ሲኮን ነው ፍጥጫው የሚመጣው፡፡ “ተነስ…የማይነሳ ህዝብ ፈሪ ነው፣ ዘላለም በፍርሃት የተጨማደደ” ተብሎ የሚፃፍበትን ጋዜጣ ግን ጋዜጣ ነው ብዬ ለመቀበልም፣ ለመናገርም ይቸግረኛል፤ ሙያውን ስለማውቅ፡፡
የእዚህ ዓይነት መገናኛ ብዙሃን ዓላማ ህዝቡ በመንግስትና በተቋማት ላይ እምነት እንዲያጣ ማድረግ  ነው፡፡ ተቋማትም ሆነ መንግስት የሚሻሻለው ግን ሚዲያው የጉዳዩ ባለቤት ሲያደርገው ነው፤ “እንዲህ አስተካክል” ሲለው እንጂ አሁን በሚታየው መንገድ አይደለም፡፡ በመንግስት ወገን የሚደረገውም ትክክል ነው እያልኩ አይደለም፡፡ እኔ መንግስትን ብሆን ጋዜጦቹን አልነካቸውም ነበር፡፡ በሌላ በኩል ግንበውጭ አገር ያሉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ነን ባዮች አይዋጡልኝም፡፡ ትክክለኛውን የጋዜጠኝነት ሙያ ተከትሎ የሚሠራ ሚዲያን አይፈልጉም፡፡ በሀገሪቱ ውስጥ ሁከት የሚያመጣን ነው የሚደግፉት፡፡
በዛሚ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያ “የጋዜጠኞችየክብ ጠረጴዛ” ፕሮግራም ላይ ጋዜጦችና የጋዜጠኞች ማህበር ከውጪ ተቋማትና ከፖለቲካ ፓርቲዎች ገንዘብና ድጋፍ ያገኛሉ የሚሉ ውንጀላዎች ይሰነዘራሉ፡፡ በዚህም ዛሚ ወንጃይ ሆኗል በሚል የሚተቹ ወገኖች አሉ፡፡
ይሄ ውንጀላ አይደለም፡፡ ዛሚም እኮ የሚዲያ ተቋም ነው፡፡ ዛሚም እኮ ሁኔታውን ያያል፣ የማይደራድርባቸው መርሆዎች አሉት፡፡ በዚህም ምክንያት ገንዘብና ድጋፍ አይደረግለትም፡፡ ከዚህ ቀደምም የተጠየቅንበት ሁኔታ ነበር፡፡ ገንዘቡ እንዳለ፣ ገንዘቡ እንደሚመጣ አውቃለሁ፡፡ የጋዜጠኞች የክብ ጠረጴዛ አላማም ሙያችን፣ ኢንዱስትሪው በጠንካራ እና ትክክለኛ መሠረት ላይ እንዲገነባ ብቻ ሳይሆን እንደዚህ ዓይነት ነገሮችን ህብረተሰቡ እንዲያውቅ ማድረግም ነው፡፡
በቀደም ዕለት በክብ ጠረጴዛ ፕሮግራም ላይ ከፖሊስ ያገኘሁትን መረጃ አውርቻቸዋለሁ፡፡ ከኬንያ የመጣው የ“አርቲክል 19” ሰውዬ… ኬንያዊ ያደረጉት እኮ… “አርቲክል 19” ነጭ አጥተው አይደለም፡፡ ነጩ ከመጣ  መንግስት ሊያየውናአይኑን ሊጥልበት ይችላል ብለው ነው፡፡ ይሄኛው ግን  ቪዛም አያስፈልገውም በሚል ነው መርጠው የላኩት፡፡ ይሄ ሰውዬ  አምስት ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ተመላልሷል፡፡ የተወሰኑ ጋዜጠኞችን ብቻ ነው የሚያሰለጥነው፡፡ ውጭ አገር የሚወስዱት፣ ትልልቅ ሆቴሎች ውስጥ ስብሰባ የሚያደርጉት ከተወሰኑ ጋዜጠኞች ጋር ብቻ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ለኢትዮጵያ ጋዜጠኞች እድገት አይጠቅምም፡፡
የፕሬስ አዋጁ ሲረቀቅ ሸራተን በተደረገው ስብሰባ “አርቲክል 19” የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ ይነገራል፡፡ ይሄ እውነት ከሆነ የአሁኑ ስልጠና ለምን እንደ ወንጀል ተወሰደ?
“አርቲክል 19” ቶቢ ሜንደ የተባለ ባለሙያ በመላክ በኤክስፐርት ደረጃ እገዛ አድርጓል፡፡ ገንዘብ ግን አልሰጠም፡፡ ተቋሙ አዲስ አበባ ጋዜጠኞች አሰለጥናለሁ ብሎ ለምንድን ነው የተመረጡት ጋዜጠኞችን  ብቻ የሚወስደው? ለምንድን ነው ስልጠናውን በድብቅ የሚያካሂደው? ለሁሉም አዲስ አበባ ላሉ ጋዜጠኞች (ለየተቋማቱ) ደብዳቤ ልኮ ሥልጠናውን መስጠት ይችል ነበር፡፡ እነማን ናቸው የተመረጡት? ምንድን ናቸው? በመንግስት ቦታ ብትሆኑ እኮ አስተያየታችሁ ሌላ ይሆናል፡፡ ሰውየው እኮ ገንዘብ እያመጣ ይሰጣል፡፡ ይሄ ምን ሊባል ይችላል? “የጋዜጠኞች የክብ ጠረጴዛን” አነሳችሁ እንጂ… ግብፅና ኤርትራ በግልጽ እኮ ነው የተናገሩት፡፡ ምንም አይነት መንገድ ተጠቅመን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለመረጋጋትን እንፈጥራለን ብለዋል፡፡ ከዚህ በፊትም ለኢሳት ገንዘብ መስጠታቸውን እናውቃለን፤ በተጨባጭ የተረጋገጠ ነው፡፡ ሁላችሁም ተጠንቀቁ ነው የምንለው፡፡ በዳያስፖራው ውስጥ ከፍተኛ ገንዘብ በማንቀሳቀስ ለመበጥበጥ የተዘጋጁ አሉ፡፡ በዚህች አገር ውስጥ ህገወጥ እንቅስቃሴ ለማድረግ ፈቃደኛ ለሆኑ ሰዎች ገንዘብ ተዘጋጅቶ ተቀምጧል፡፡ ስለዚህ በሉዓላዊነታችሁ ላይ አትደራደሩ፡፡ ማንም ሚዲያ የአገሩን ጥቅም አሳልፎ እንዳይሰጥ…እንላለን፡፡
በተለያዩ የህትመት ውጤቶች ላይ “የጋዜጠኞች ክብ ጠረጴዛን” ተቃውመው ሲጽፉ አያለሁ፤ መንግስትን የሚደግፍ በሚል፡፡ መንግስትን ደገፉ የሚባለው “ልማትህን ጠብቅ፣ ከድህነት የምትወጣው በልማት ላይ ስትተጋ ነው” ስለምንል ነው፡፡ ይሄን ለማለት የመንግስት ደጋፊ መሆን አይጠይቅም፡፡ ወደ አገሬ የመጣሁት ይሄን ልሠራ ነው፡፡ አሜሪካንን ትቼ የመጣሁት ጠንካራና የበለፀገ “ቫይብራንት” የሆነ የሚዲያ ኢንዱስትሪ ለመገንባት ነው፡፡ መንግስትን መቆጣጠር የሚችል፣ የመንግስት ጠላት ሳይሆን እንደ አንድ ተቋም የህዝብን ደህንነት በጋራ የሚጠብቅ ሚዲያ ለመፍጠር ነው፤
ጋዜጠኝነት፤ ልማታዊ የሚባል ቅፅል አያስፈልገውም፡፡ ጋዜጠኝነት በራሱ ልማታዊ ነው፡፡ እኔ “የፖለቲካ” ወይም “የታይብሎይድ” ጋዜጠኝነት በሚል በሚሰጠው ቅፅል ተስማምቼ አላውቅም፡፡ ጋዜጠኝነት “ኢንስትሩመንት ፎር ሂዩማን ቢንግ” (ለሰው ልጅ የሚያገለግል እንደማለት) ብዬ ነው የምከራከረው፡፡
ከኤርትራና ከግብፅ ገንዘብ ወስደዋል ብላችሁ ተናግራችኋል፤ ገንዘቡ መቼ ተሰጠ? ለማን ተሰጠ? እንዴት ተሰጠ?
እኛ እኮ ያንን የተናገርነው ከፖሊስ መረጃ ነው፡፡ የፖሊስ መረጃ ከተለያዩ አካባቢዎች ፈንድ በተለይ ከውጪ እንደሚደረግ ነው የጠቀሰው፡፡ የሆነ ሆኖ ግን ሃገሪቱን ለማተራመስ ቅርጫት አስቀምጠው የሚለምኑ ወገኖች እንዳሉ እናውቃለን፡፡
እነማን ናቸው ይሄን የሚያደርጉት በስም እንወቃቸው
እንዴ! ብርሃኑ ነጋ ከግብፅ ተቀብሎ በኢሳት ሲታይ አልነበረም እንዴ?
ብርሃኑ ነጋ መቀበሉ እነዚህን የሃገር ውስጥ ሚዲያዎች እና አክቲቪስቶች ለመወንጀል እንዴት ያስችለናል?
አይደለም! እኛ እኮ ሃሳብ የሰጠነው ሲቀባበሉ በዓይናችን አይተናል ብለን አይደለም፡፡ ከአርቲክል 19 ጋር በስውር ሲንቀሳቀሱ ከፖሊስ መረጃ ማግኘታችንን ነው የተናገርነው፡፡
በአጠቃላይ በዚህች ሃገር ውስጥ የጎዳና ላይ ነውጥ እንዲካሄድ ግፊት የሚያደርጉና ገንዘብ የሚያሰባስቡ ሃይሎች እንዳሉ የታወቀ ነው አልን እንጂ እነሱ ተቀብለዋል የሚል ውንጀላ አላቀረብንም፡፡ ልንልም አንችልም፡፡ የጎዳና ላይ ነውጥ የሚናፍቁ ወገኖች ገንዘብ እንዴት እንደሚያገኙ ነው የተናገርነው፡፡ ይሄ ደግሞ በአለማቀፍ ደረጃ የሚታወቅ መረጃ ነው፡፡ እኛ ገንዘብ ሲቀበሉ አይተናል የሚል ቃል አልወጣንም፡፡
ከዚህ ቀደም ሪፖርተርስ ዊዝ አውት ቦርደር የአንቺን ፕሮግራም ስፖንሰር ያደርግ ነበር ዛሬ ላይ ከእነዚህ ተቋማት ገንዘብ ተቀብሎ መስራቱን እንዴት ትኮንያለሽ?
በድብቅ ሲሆን ነዋ! እኛ እኮ በግልፅ እየተናገርን ሪፖርተርስ ዊዝ አውር ቦርደርስ ገንዘብ ሰጥቶናል ብለን ተናግረን ነው የተጠቀምነው፡፡ አሁን ግን በድብቅ ጋዜጠኞችን በየሆቴሉ ሰብስቦ ሰጠ  የሚል ነው ከፖሊስ ያገኘነው መረጃ፡፡
በሰብአዊ መብትና በሚዲያ ጉዳይ ላይ የሚሰሩ አለማቀፍ ተቋማት ሁሉም መንግስትን ይተቻሉ፡፡ ይሄ መንግስት ጋር ድክመት መኖሩን አያሳይም?
አንድ አይነት ትችት የሚያቀርቡት ምንጫቸው አንድ አይነት ስለሆነ ነው፡፡ ፍልስፍናቸው፣ ተልእኮአቸው፣ የገንዘብ ምንጫቸው አንድ አይነት ነው፡፡ ስለዚህ አንድ አይነት ነው ሊያወሩ የሚችሉት፡፡
ለኢህአዴግ ትወግናለች ኢህአዴግም ነች ትባያለሽ አንቺ ደግሞ ማስረጃ የሌለው ውንጀላ ነው ትያለሽ፡፡ እናንተስ ፕሬሶችንና ጋዜጠኞችን የውጭ ሃይሎች ተላላኪ ናቸው ስትሉ ያለ ማስረጃ መወንጀል አይሆንም?
እኔ ላይ ማስረጃ ማንም ሊያቀርብ አይችልም፡፡ እኔ ሚዲያ ነኝ፡፡ ሚዲያ ደግሞ ትልቁ መርሁ ገለልተኛነት ነው፡፡ እኔ ፖለቲከኛ ሆኜም አላውቅም፡፡ ልሆንም አልችልም፡፡ እኔ ላይ የሚቀርበውን ውንጀላ ያመጣው ሻዕቢያ ነው፡፡ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጊዜ ዜናውን መጀመሪያ ይፋ ያደረኩት እኔ ነኝ፡፡ ወረራ የተፈፀመው ኤርትራ ጦር እንደሆነ በመናገሬ፣ በወቅቱ  የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ሱዛን ራይትስ የኤርትራ ጉዞዋን ልትሰርዝ ችላለች፡፡ ስለዚህ የእኔን ተአማኒነት ለመሸርሸር ነው ሻዕቢያ ይሄን ዘመቻ የጀመረው፡፡ ነገር ግን እኔ በራሴ ስለምተማመን ስራዬንም ህዝብ የሚያየው ስለሆነ የሚያስጨንቀኝ ነገር አይደለም፡፡
አንቺስ ያለማስረጃ ወንጃይ አልሆንሽም ወይ ለተባለው እኛ በመጀመሪያ ደረጃ እገሌ እንዲህ አድርጓል ብለን አይደለም የምንናገረው፡፡ ፖሊስ የሰጠንን መረጃ ነው የተናገርነው፡፡
በተደጋጋሚ በክብ ጠረጴዛ ፕሮግራሞች ላይ ፕሬሶቹ ገለልተኛ እንዳይሆኑ ያደረጋቸው ገንዘብ ከፓርቲ ስለሚቀበሉ ነው የሚሉ ትችቶችንና ውንጀላዎችን ታቀርቢያለሽ፡፡ ለዚህ ማስረጃ አለሽ?
መልስ ነው የሃገራችን ፕሬሶች የሙያውን መርህና ስነ ምግባር ተከትለውመንቀሳቀስ አለባቸው ነው የምንለው
ከገንዘብ ጋር የተያያዘ ነገር ይነሳል፣ ከፓርቲ ፈንድ ይደረግላቸዋል ትላላችሁ ለዚህ ማስረጃ አላችሁ ወይ ነው ጥያቄያችን?
እኛ እንደዚያ ብለን አልፈረጅንም፡፡ ነገር ግን እንደዚህ አይነት ነገሮች በሌላው አለም እንዴት ነው የሚስተናገዱት የሚለውን በልምድም እናውቀዋለን ነው ያልነው እንጂ ተቀብለዋል የሚል መደምደሚያ ያለው ነገር አልተናገርንም፡፡ ያለውንና የምናውቀውን ሁኔታ እየተናገርን ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ነው መልእክት የምናስተላልፈው፡፡ ጋዜጦች የፖለቲካ ፅንፍ መያዝ ይችላሉ ብለናል ነገር ግን በሙያው ስም መጠቀም የለባቸውም ነው መከራከሪያችን፡፡ የተቃዋሚ ድርጅት ልሳን ነኝ ብሎ ራሱን ይፋ ማድረግ እንጂ በመገናኛ ብዙሃን ስም ማጭበርበር አይቻልም፡፡ አክቲቪዝም እና ጋዜጠኝነት መለያየት አለባቸው ነው የኛ አቋም፡፡ ትችት ለምን ታቀርቢያለሽ ከሆነ እነሱም እኮ በኛ ላይ ብዙ ነገር ይፅፋሉ ይተቻሉ፡፡ እኔ እንደውም አሉባልታቸው ሲበዛ ነው ከሙያው ስነምግባር ጋር እያጣቀስኩ መተቸት የጀመርኩት፡፡

         ተስፋለም ወልደየስን በጋዜጠኝነቱ እና በኢትዮጲያ የአካባቢ ጥበቃ ጋዜጠኞች አባልነቱ ምክንያት ከትውውቅ ያለፈ ጓደኝነት አለን፡፡ ከጀርባው የማትለየው ላብቶፑን አዝሎ ፈጠን ፈጠን እያለ በንቃት የሚንቀሳቀስ ለጋዜጠኝነት ሙያ ትልቅ ፍቅር እና ክብር ያለው ነው፡፡ ሙያው ልክ ተሳክቶላቸዋል በሚባሉ አገሮች ደረጃ  እንዲሆን ሁልጊዜም የሚመኝ ብቻ ሳይሆን ቅናቱን ለአፍታም ከመግለፅ የማይቆጠብ ነው፡፡ በየትኛውም መገናኛ ብዙሀን አሪፍ ነገር ተሰራ ሲል ያንን ከመናገር ወደ ሃላ የማይል የሰራውንም ሰው ማበረታታት ደስ የሚለው ነው፡፡
በህዳር ወር በኢትዮጲያ የተካሄደውን የሚዲያ ፎረም ማጠቃለያ የሆነውን ሰነድ ለአዘጋጇ ለኢትዮጲያ ለማስረከብ እና የቀጣዩን የሚዲያ ፎረም አዘጋጅ እና የፎረሙን መሪ ቃል ለማሳወቅ በኢሊሊ ሆቴል ባለፈው ሳምንት ረቡእ በተካሄደው ዝግጅት ላይ ከተስፋለም ጋር ተገናኝተናል፡፡ ምነው ጠፋሽ በሚል  ክፉኛ ወቀሰኝ፡፡ ስልኬን አትመልሺም  ብሎም ማዘኑን ነገረኝ ተለያየን፡፡ በማግስቱ ለአርብ ምሳ ለመብላት ተቀጣጠርን፡፡
አርብ እለት በቀጠሮአችን መሰረት ካዛንችስ በሚገኘው ሮሚና ሬስቶራንት በስድስት ተኩል ተገናኘን፡፡  ምሳ እየበላን ብዙ ነገሮችን አወራን፡፡ ልክ ሁልጊዜ እንደሚለው ሲኒሮቻችን የሆናችሁ ጋዜጠኞች ሙያውን ለምን ጣል ጣል ታደርጉታላችሁ አለና የተለመደውን የፕሮፌሽናሊዝም የኤቲክስ ጉዳዮችን አወራኝ፡፡ ፌስቡክ እንዴት እሱ የሚመኘውን ጋዜጠኝነት እየተገዳደርው እንደሆነ አዲስ ወደ ሙያው የሚገቡ ልጆች ኮትኳች እያጡ እንደሆነም ሲያወራኝ ነበር፡፡ ከዛም ሁለታችንም በቅርበት ስለምናውቀው በቅርብ አሜሪካን አገር ስለሄደ ልጅ አነሳንና ጨዋታችንን ቀጠልን እኔ የማዝነው  እሱን የመሰለ ልጅ አሜሪካን  ሲቀር አያሳዝንም እንዴት ይቀራል ብሎ በውስጡ የተፈጠረበትን ጥያቄ ጠየቀኝ፡፡
አባይን ለመጎብኘት ለጋዜጠኞች በተዘጋጀው የቅርብ ጊዜ ጉብኝትም ተስፋለም ተሳታፊ ስለነበርበተለይ በለስ ስለምትባል እናከተቆረቆች አስራ ሶስት አመት ስለሆናት ከተማ በስሜት ሲያወራኝም ነበር፡፡ አርቲስት ጆሲ ለማንአልሞሽዲቦ የሰራውን ፕሮግራምም በአድናቆት አውርቶኛል፡፡ ሰሞኑን እየተካሄደ በነበረው የጣና ፎረም ላይ ለመገኘት ፈልጎ የምዝገባው ጊዜ ስላመለጠው በቁጭት አውርቶኛል፡፡
ከምሳ በሃላ ቡና ለመጠጣት እዛው ካዛንችስ ሙንሽ ካፌ ገባን፡፡ የቴዲ አፍሮን ኮንሰርት እንዲያመልጠኝ አልፈልግም፡፡ ቴዲ እንዲህ አለ ተመልካቹ እንዲህ አለ የሚለውን ራሴ ማየት አለብኝ አለና ለጋዜጠኞች መግቢያ የያዙ ሰዎች ጋር ደወለ፡፡ ኤልሳቤት እቁባይም ትፈልጋለች አላቸው፡፡ ስልኩን ከዘጋው በሃላ እኔ ማምሸት ስለማልችል ካርዱን ትወስደዋለህ ስለው የስ ሰው እጋብዝበታለሁ አለኝ፡፡ ሌላ ቀጠሮ ስለነበረው ወደ ብሄራዊ ቲያትር ከመሄዱ በፊት እዛው ካዛንችስ ጫማ እያስጠረግን አንድ ጋዜ ማንበብ ጀመረ ጋዜጣው የአንድን ሰው ፎቶ አሳስቶ አውጥቶ ነበርና በሱ ተሳስቀን ይህህን ስካን አድርጌ እልክለታለሁ ሲል እኔ ደግሞ እባክህ እንደጋዜጣው አታርጅ በለው ብየው ተለያየን፡፡ ከዛ በሃላ ተስፋለም በፀጥታ ሀይሎች እንደተያዘ የሰማሁት ቅዳሜ ጠዋት ፌስቡክ ላይ ነው፡፡

የከፋ ጉዳት የደረሰው በአምቦ፣መደወላቦ እና ሐረማያ ነው
ተቃውሞው እስከ ሃሙስ በመንግስት ሚዲያ አልተነገረም

አዲስ አበባንና በዙሪያዋ የኦሮሚያ ከተሞችን በማካተት የተዘጋጀውን የጋራ ማስተር ፕላን የሚያወግዙ የክልሉ ተማሪዎች፤ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ሲያካሂዱት በሰነበቱት ተቃውሞ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ከፖሊስ ጋር በተፈጠረ ግጭት የበርካታ ሰዎች ህይወት ጠፋ፡፡ በትንሹ ወደ መቶ የሚጠጉ ሰዎችም እንደቆሰሉና ጉዳት እንደደረሰባቸው ታውቋል፡፡ በተቃውሞዎቹ ዙሪያ ቀጥተኛ ዘገባ ሲያስተላልፍ የነበረው የመንግስት ሚዲያ ሐሙስ እለት ከመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጽ/ቤት የወጣውን መግለጫ ያቀረበ ሲሆን በአምቦና በመደወላቡ 3 ተማሪዎችን ጨምሮ 7 ሰዎች እንደሞቱ አትቷል፡፡ ሲኤንኤንና ሌሎች የሚዲያ ተቋማት በርካታ ሰዎች መሞታቸውን በመጥቀስ የተለያዩ ዘገባዎችን ያሰራጩ ሲሆን የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ 30 ሰው መሞቱን እንደተናገሩ ጠቅሰዋል፡፡ የእግር ኳስ ጨዋታ በቴሌቭዥን የሚመለከቱ የሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ በተወረወረ ፈንጂ አንድ ተማሪ እንደሞተና 70 ሰዎች እንደቆሰሉም መግለጫው አስታውሶ፤ ዩኒቨርስቲዎች እንደተረጋጉ መንግስት ቢገልፅም በስልክ ያነጋገርናቸው የዪኒቨርሲቲ ተማሪዎችና መምህራን ግን ግጭቱና ውጥረቱ እንዳልበረደ ተናግረዋል፡፡
በአዳማ፣ በጅማ፣ ሃሮማያ፣ አምቦ፣ ነቀምት፣ መደወላቡ እና ድሬደዋ ዩኒቨርሲዎች በተነሳው ተቃውሞ እስካሁን ከተገለጸው በላይ የሞትና የአካል ጉዳት በተማሪዎች ላይ እንደደረሰ የየአካባቢው ምንጮች የገለፁ ሲሂን፣ በርካቶች እንደታሰሩም ጠቁመዋል፡፡ በሃሮማያ ፍንዳታ የሞቱት ተማሪዎች ሁለት መሆናቸውን የገለፁ ምንጮች፣ በብሄር ተወላጅነት የተቧደኑ ተማሪዎች ጎራ ለይተው በፈጠሩት ግጭት በርካታ ተማሪዎች እንደተደባደቡ ተናግረዋል፡፡
አዲስ አበባንና በዙሪያዋ ያሉ ከተሞችንም ያስተባብራል ተብሎ የጋራ ማስተር ፕላን የተዘጋጀው ከከተማ አስተዳደርና ከአሮሚያ ክልል መስተዳደር ተውጣጥቶ በተቋቋመ ቡድን ሲሆን፤ ፕላኑን የተቃወሙ ተማሪዎች “የኦሮሚያ መሬትን የሚቆርስ ህገ መንግስቱን የሚፃረር ነው፡፡ ሃገራችንን ትተን ወዴት እንሂድ!” የሚሉ መፈክሮችን አሰምተዋል፡፡
ማክሰኞ ማታ በአዳማ ዩኒቨርሲቲ የጀመረው ተቃውሞ፤ ረቡዕ እለት ከምሳ በኋላ ረገብ ቢልም ማተሚያ ቤት እስከገባንበት ሰዓት ድረስ ውጥረቱ እንደነበር ለማወቅ ችለናል፡፡ የመማር ማስተማር ትምህርት እንደተቋረጠና ወደ ግቢ መግባት እንጂ መውጣት እንደተከለከለ የገለፁት ምንጮች፤  አንዳንድ ተማሪዎች በአጥር ሾልከው እየወጡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በሃረማያ ዩኒቨርሲቲ ረቡዕ ከምሽቱ 3 ሰዓት ላይ በቴሌቪዥን እግር ኳስ ሲመለከቱ የነበሩ ተማሪዎች ላይ የፈንጂ ጥቃት ከደረሰ በኋላ የተቀሰቀሰው ሁከት ብሄር ወደ ተቧደነ ግጭት እንደተለወጠ የጠቆሙት ምንጮች፤ ግጭቱ ከፌደራል ፖሊስ ከቁጥጥር ውጪ እስከ አርብ ድረስ እንዳልበረደ ጠቁመዋል፡፡
ከዩኒቨርሲቲው መውጣትና መግባት ተከልክሎ ቢቆይም፣ ወደ ቤተሰቦቻችን እንመለስ የሚሉ ተማሪዎች በመበራከታቸው ትናንት አርብ ከሰአት በኋላ ጀምሮ እንዲወጡ ተፈቅዷል፡፡
የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ያነሱት ተቃውሞ ከሌሎች የጠነከረ እንደነበር የጠቆሙት ምንጮች፤ ተቃውሞው ከዩኒቨርሲቲም ውጭ እንደተስፋፋ ገልፀዋል፡፡ 25ሺ ያህል ሰዎች ከተቃውሞ ወደ አደባባይ መውጣታቸው የተዘገበው አል አፍሪካ፤ ከባድ ግጭት መከሰቱን አትቷል፡፡ በተጨማሪ መረጃ ባይረጋገጥም፣ ከአካባቢው ነዋሪዎች ግን 30 ሰዎች መሞታቸውን ተናግረዋል ሲኤ ሲሴን ኤን የዘገበ ሲሆን፤ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት ሐሙስ ባወጣው መግለጫ የሟቾች ቁጥር 7 እንደሆነ ጠቅሶ በመደወላቡ ዩኒቨርሲቲ በተነሳው ተቃውሞ ከገለልተኛ ወገኖች ማረጋገጥ ባይቻልም መንግስት 3 ተማሪዎች መሞታቸውንና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን አስታውቋል፡፡ በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ጉዳት ስለመድረሱ የተባለ ነገር የለም፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 6 ኪሎ ካምፓስ፤ ሐሙስ ጠዋት ተማሪዎች ወደ ግቢ መግባትም መውጣትም ተከልክለው ነበር፡፡ የፌደራል ፖሊስ አባላትም በቡድን በቡድን በአካባቢው ሲንቀሳቀሱ የነበረ ሲሆን ከሰዓት ለተቃውሞ የተሰበሰቡ ተማሪዎች የተለያዩ መፈክሮችን አሰምተዋል፡፡  
ከፖሊስ ጋር የተፈጠረ ግጭት ያልነበረ ሲሆን ተቃውሞ ሲያሰሙ የነበሩት ተማሪዎች ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር የሚወያዩበት መድረክ እንደሚዘጋጅ የዩኒቨርሲቲው ኃላፊዎች መናገራቸውን ምንጮች ገልጸው፤ በዚሁ ምክንያት ከፖሊስ ጋር ግጭት አለመፈጠሩን ጠቁመዋል፡፡  
መንግስት በበኩሉ፤ ተቃውሞውና ግጭቱ ጥቂት ጸረ ሰላም ሃይሎች በሚያሰራጩት አሊባልታ ምክንያት የተፈጠረ ነው በማለት በሁከቱ ጉዳት መድረሱ እንዳሳዘነው ገልጿል፡፡  
አንድነት ፓርቲ ትናንት “በአፅንኦት እናወግዛለን” ሲል ባወጣው መግለጫ፤ መሬት በግል አለመያዙ ብዙ ችግሮችን እያስከተለ እንደሆነ ገልጿል፡፡ የተቃውሞ ድምፅ በሚያሰሙ ሰዎች ላይ መንግስት የሚወስደውን እርምጃ እንደሚያወግዝም ፓርቲው አስታውቋል፡፡

Published in ዜና

            ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ጋዜጠኞችና የድረገፅ ፀሃፊዎች (ጦማሪዎች) በአንድ ጊዜ ተይዘው ለእስር ሲዳረጉ የአሁኑ የመጀመሪያው ነው፡፡ እስሩን በመቃወም ኢንተርኔት ተጠቃሚ ኢትዮጵያዊያን ከእስከዛሬው ሁሉ የበለጠ ድምፅ ማሰማታቸውን ቢቢሲ የዘገበ ሲሆን፤ ዋና ዋናዎቹ ዓለማቀፍ የመብት ተሟጋችና የፕሬስ ነፃነት ተቋማት “የአፈና ዘመቻ ነው” በማለት አውግዘዋል በመንግስት ላይ ተፅእኖ እንዲያሳድሩ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጥሪ የቀረበላቸው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ጆን ኬሪ እስረኞቹ መፈታት ይገባቸዋል ብለዋል፡፡ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር በበኩላቸው ሀሳባቸውን በነፃነት በመግለፃቸው ብቻ ነው የታሰሩት በማለት የመንግስትን እርምጃ ተቃውመዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ግን የፕሬስ ነፃነት ይከበር የሚል ጥቅል መግለጫ ከማውጣቱ በስተቀር ስለታሰሩት ሰዎች አላነሳም፡፡ የጋዜጠኞችና የፀሐፊዎች እስር አሳሳቢነት ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን በዓለም ደረጃ ሲያነጋግር ቢሰነብትም፣ የመንግስት አካላትና የመንግስት ሚዲያ አንዳችም መረጃ ያልሰጡበት ምክንያት አልታወቀም፡፡ ጋዜጠኞችና ፀሐፊዎች ላይ ክስ የሚቀርብ ከሆነ በእስር ማቆየት እንደማያስፈልግና በዋስ መለቀቅ እንዳለባቸው የፕሬስ ህጉ ላይ የተጠቀሰ ቢሆንም፤ ዘጠኙ ጋዜጠኞች ፀሐፊዎች የዋስ መብት አልተፈቀደላቸውም፡    
ባለፈው ሳምንት አርብ ምሽትና ቅዳሜ ካሉበት በፀጥታ ሃይሎች ተይዘው የታሰሩት ጋዜጠኞችና ፀሃፊዎች፤ ኢትዮጵያ ውስጥ አለመረጋጋትን ለመፍጠር አስበዋል የሚል ጥርጣሬ እንዳለው ፖሊስ ለፍ/ቤት ገልጿል፡፡ በዚህም ታሳሪዎቹ ከዓለም አቀፍ መብት ተሟጋች ተቋም ጋር በገንዘብና በሃሳብ በመተባበር ወይም በኢንተርኔት ማህበራዊ ድረገፆችን በመጠቀም ተንቀሳቅሰዋል-ብሏል ፖሊስ፡፡ የትኛው አለማቀፍ የመብት ተቋም እንደሆነ በስም ያልገለፀው ፖሊስ፤ ታሳሪዎቹ አለመረጋጋትን ለመፍጠር የፈፀሙት ተግባር ካለም ምን ምን እንደሆነ አልጠቀሰም፡፡ ፖሊስ የምርመራ ጊዜ እንደሚያስፈልገው በመጠየቁ በእስር እንዲቆዩ የተደረጉት ጸሐፊዎችና ጋዜጠኞች ከህግ ባለሙያ ወይም ከቤተሰብ ጋር እንዲገናኙ አልተፈቀደላቸውም ተብሏል፡፡
ሦስቱ ጋዜጠኞች፣ በቀድሞው አዲስ ነገር፤ የእንግሊዝኛው ፎርቹንና አዲስ ስታንዳርድ ላይ በፍሪላንሰርነት ይሰራ የነበረው ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ፣ የአዲስ ጉዳይ መፅሄት ከፍተኛ አዘጋጅ አስማማው ኃይለጊዮርጊስ የቀድሞ አዲስ ዘመን ጋዜጠኛ ኤዶም ካሣዬ ናቸው፡፡ ኤዶምን ጨምሮ አቤል ዋበላ፣ ዘላለም ክብረት፣ በፍቃዱ ኃይሌ፣ ማህሌት ፋንታሁን፣ ናትናኤል ፈለቀ እና አጥናፈ ብርሃኔ “ዞን ዘጠኝ” በመባል የሚታወቁ የድረገፅ ፀሐፊዎች (ጦማሪዎች) ናቸው፡፡
ግራ የገባቸው የጋዜጠኛ ማህበራት
መንግስት አፈናውን ለማጠናከር በአዲስ ዙር የእስር ዘመቻ እያካሄደ ነው በማለት ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋችና የፕሬስ ነፃነት ድርጅቶች ተቃውሟቸውን ቢገልፁም፣ የአገር ውስጥ የጋዜጠኞች ማህበራት በበኩላቸው ግራ በመጋባት ሲዋልሉ ነው የሰነበቱት፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጋዜጠኞች ህብረት ሊቀመንበር አቶ አንተነህ አብርሃም፤ ባለፈው ማክሰኞ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፤ “ታሣሪዎቹ ጋዜጠኛ ስለመሆናቸውና ከስራቸው ጋር በተገናኘ ስለመታሠራቸው ማጣራት ስላለብን፤ ለጊዜው ምንም ዓይነት የአቋም መግለጫም ሆነ ማብራሪያ ለመስጠት ይቸግረናል” ብለዋል፡፡
ከአንድ ቀን በኋላ ሐሙስ እለት ማህበሩ ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫ ግን፤ መንግስት ጋዜጠኞቹ እና ጦማሪዎቹ ስለታሠሩበት ጉዳይ ይፋዊ መግለጫ አለመስጠቱ እንዳሣሠበው አመልክቷል፡፡ “በጉዳዩ ላይ የመንግስት ዝምታ አሳስቦናል፤ ከመንግስት የጠራ መረጃ እንፈልጋለን” ያሉት አቶ አንተነህ፤ “ፍ/ቤት ስለቀረቡበት ሁኔታም ከመንግስት የጠራ መረጃ አለማግኘታችንም ያስጨንቀናል” ብለዋል፡፡ ማህበራቸው እንዲሁም የምስራቅ አፍሪካ ጋዜጠኞች ህብረትና የአለማቀፉ የጋዜጠኞች ፌደሬሽን፣ የእስረኞቹን ጉዳይ በትኩረት እንደሚከታተሉት አቶ አንተነህ ገልፀዋል፡፡
በሌላ በኩል “ዩኔስኮ ጦማሪዎች ጋዜጠኞች አይደሉም ብሎ ፈርጇል፣ በኢንተርኔት የማህበራዊ ድረገፅ ሚዲያውም ሃላፊነት የሚሠማው አይደለም፤ ከዚህ አንፃር ለእነዚህ አካላት ጥበቃ ማድረግ እንዴት ይቻላል?” ሲሉ ይጠይቃሉ፤ አቶ አንተነህ፡፡
“ጋዜጠኞቹ የታሠሩት ከሙያቸው ውጪ በሆነ ጉዳይ ከሆነ መንግስት በህግ መጠየቅ ይችላል፤ ጉዳዩን ግን እንከታተላለን፡፡ ከሙያቸው ጋር በተገናኘ ከሆነም ጠበቃ አቁመን ከመከራከር ባለፈ፤ የአለማቀፍ ጋዜጠኞች ህብረትን አስተባብረን መንግስትን ስለጉዳዩ አጥብቀን እንጠይቃለን” ብለዋል አቶ አንተነህ፡፡
የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማህበር ሊቀመንበር አቶ መሠረት አታላይ በበኩላቸው፤ “እኛ በጋዜጠኝነት አናውቃቸውም፤ ጋዜጠኞችም አይደሉም፤ ብሎገሮች (ጦማሪዎች) ናቸው፤ በእነሱ መታሠር ጉዳይ እኛ የምናውቀው ነገር የለም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
“ሠሞኑን ከታሠሩት መካከል በጋዜጠኝነት የማውቀው ተስፋለም ወልደየስን ብቻ ነው” ያሉት የኢትዮጵያ ነፃ ጋዜጠኞች ማህበር ሊቀመንበር አቶ ወንድወሰን መኮንን፤ “ስለ ዞን 9 ፀሀፊዎች የጠራ መረጃ የለኝም፤ ጦማሪዎች በዩኔስኮ ድንጋጌ መሠረት ጋዜጠኛ አይባሉም፣ ስለጦማሪያኑ መሟገት ቢቸግረንም ስለጋዜጠኛው እስር እና ስለጉዳዩ መንግስት ለህዝብ መግለጽ አለበት” ብለዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በሽብርተኝነት እየተከሰሱ የተፈረደባቸው ጋዜጠኞችም፤ ለመንግስት ያቀረቡት የምህረት ጥያቄ ከግንዛቤ ገብቶ፤ ከእስር እንዲለቀቁ መንግስትን እንደሚጠይቁ አቶ ወንድወሰን ተናግረዋል፡፡
ጋዜጠኞቹና ፀሃፊዎቹ መታሰራቸው እንዳሳሰበው የገለፀው አዲስ በመቋቋም ላይ ያለው የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ (ኢጋመ)፤ መንግስት የታሰሩበትን ጉዳይ ለህዝብ ይፋ እንዲያደርግና ጋዜጠኞቹ እንዲለቀቁ ጠይቋል፡፡   
ጠንካራ የጋዜጠኛ ማህበር በሌለበት አገር፣ ጋዜጠኞችና ጦማርያን ለእስር መዳረጋቸው አሳዛኝ ነው ያሉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ፤ ሃሳብን በነፃነት መግለፅ ባልተከበረበት ሀገር የፕሬስ ቀንን ማክበር ለውጭ መንግስታት ድጋፍ ማግኛ ካልሆነ በስተቀር ትርጉም የለሽ ነው ሲሉ ተችተዋል፡፡ “የፕሬስ ቀንን ማክበር ያለበት ፕሬስ ነበር፤ ነገር ግን እንኳን ሊያከብር ህልውናውንም አላረጋገጠም” ብለዋል ምሁሩ፡፡
የጋዜጠኞቹ እና የጦማርያኑ እስራት ሃሳብን መግለፅ እንደ አደጋ የሚታይበት ጊዜ መምጣቱን አመላካች ነው ያሉት ዶ/ር ዳኛቸው፤ በውይይትና በክርክር፣ በውድድርና በፉክክር ሳይሆን የአንድን ቡድን ሃሳብ ብቻ የበላይ በማድረግ ሌላው ፀጥ እንዲል እየተደረገ ነው ሲሉ ይተቻሉ፡፡
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የህግ ባለሙያ በሰጡት አስተያየት፤ የመረጃ ነፃነትን ለመደንገግ የወጣው አዋጅ፣ ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሃሳቡን የመግለፅ ነፃነት እንዳለው ይጠቅሳል ብለዋል፡፡ “ማንኛውም ሰው ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውን አመለካከት የመያዝ፣ ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት ሃሳቡን የመግለጽ ነፃነት አለው፡፡ ይህ ነፃነት ከሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጪ ወሰን ሳያደርግለት በቃል ሆነ በጽሑፍ ወይንም በህትመት በስነ ጥበብ መልክ ወይንም በመረጠው፣ ለማንኛውም የማሰራጫ ጣቢያ ማንኛውም ዓይነት መረጃ የመሰብሰብ፣ የመቀበል ሃሳብ ያካትታል፡፡ ነገር ግን የጦርነት ቅስቀሳዎች፣ ሰብዓዊ ክብርን የሚነኩ የአደባባይ መግለጫዎች በህግ የሚከለከሉ ይሆናል ይላል” ሲሉም የህግ ባለሙያው አስረድተዋል ፡፡
የጋዜጠኞቹንና ጦማሪያኑን መታሠር ተከትሎ መግለጫ ያወጣው አምነስቲ ኢንተርናሽናል፤ ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችንና ፖለቲከኞችን የማሠር ልምድ እንዳላት ጠቅሶ፤ በአዲስ የአፈና ዘመቻ የታሰሩት ጋዜጠኞችና ጦማሪዎች  በአስቸኳይ እንዲለቀቁና አለማቀፉ ህብረተሰብም ግፊት እንዲያደርግ ጠይቋል፡፡
ተቀማጭነቱን በኒውዮርክ ያደረገው የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት (CPJ) በበኩሉ፤ “ጋዜጠኞቹንና ጦማሪያኑን በማሠር የኢትዮጵያ መንግስት ሠላማዊ የሆነውን ሃሳብን የመግለጽ መብትን ወደ ወንጀል እየቀየረው ነው” በማለት ዘጠኙ ጋዜጠኞች በአስቸኳይ እንዲለቀቁ ጠይቋል፡፡
“ዞን 9” በሚል የሚታወቁት ጦማሪያን፣ የተለያዩ ዜናዎችንና ትችቶችን የሚያቀርቡ፣ የሀገሪቱ የፕሬስ አፈና የወለዳቸው ስብስቦች ናቸው ያለው ይሄው ተቋም፤ በመንግስት በኩል በደረሰባቸው ወከባ ለበርካታ ወራት ስራቸው ተስተጓጉሎ እንደነበር ገልጿል፡፡ እንደገና ስራቸውን ለመጀመር ማቀዳቸውን በገለፁበት ሳምንት ነው የታሰሩት ብሏል ተቋሙ፡፡
ጋዜጠኞችን፣ የሚዲያ ተቋማትንና አሳታሚዎችን በአባልነት ያሰባሰበው የዓለም ፕሬስ ኢንስቲትዩት (IPI) በበኩሉ፤ ባለፈው ህዳር ወር የልዑካን ቡድን ወደ ኢትዮጵያ እንደተላከ ገልፆ፤ ከመንግስት አካላትና ከጋዜጠኞች ጋር እንደተወያየ በመጠቆም፣ የአገሪቱ ሁኔታ አሳሳቢ ሆኖ አግኝቼዋለሁ ብሏል፡፡ በሽብር ህጉ ሰበብ ጋዜጠኞች መታሰራቸውን ሲቃወም እንደነበር ተቋሙ አስታውሶ፤ አሁን እንደገና አዲስ የእስር ዙር መጀመሩን አውግዟል፡፡
ተመሳሳይ ውግዘት የሰነዘረው ሂዩማን ራይትስ ዎች በበኩሉ፤ ከአፍሪካ ውስጥ ከፍተኛ ግምት ከሚሰጣቸው አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗን ጠቅሶ፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ፤ የዲሞክራሲና የመብት አከባበርን እንደወትሮው ችላ ማለት አይኖርባቸውም ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ የፕሬስ ህግና የመረጃ ነፃነት አዋጅ በተዘጋጀበት ወቅት በመንግስት ፈቃድ በሙያ ምክርና በውይይት አስተባባሪነት እንዲሳተፍ የተደረገው አርቲክል 19 የተሰኘው ዓለም አቀፍ ተቋምም እንዲሁ እስሩን አውግዟል፡፡
ብዙዎች የመብትና የፕሬስ ነፃነት ተቋማት በኢትዮጵያ እንዳይሰሩ እየታገዱ ጥቂት መቅረታቸውን የገለፀው አርቲክል 19፤ ሳይታገዱ ከቆዩት ተቋማት መካከል አንዱ በመሆኔ የፕሬስ ነፃነትን በሚመለከት ለተባበሩት መንግስታት ሪፖርት የማቅረብ በሙያውና ህጋዊ ትንታኔ በዓለም ደረጃ ከፍተና አክብሮትን እንዳተረፈ የሚነገርለት አርቲክል 19፤ ለመንግስታት የህግ ማሻሻያ ሀሳብ በማቅረብና ለጋዜጠኛው የስልጠና ድጋፍ በመስጠት ላይ ያተኮረ በመሆኑ ከመንግስት አካላት ጋር ፊት ለፊት ፍጥጫ አይታይበትም፡፡ ለብዙ ጊዜ በኢትዮጵያ ሳይታገድ የቆየውም በዚህ ምክንያት ነው ተብሏል፡፡ ባለሙያዎችን እየላከ ጋዜጠኞች ስልጠና እንዲያገኙ ይተባበር እንደነበረም የሚታወቅ መሆኑን ተቋሙ አመልክቶ፣ ለበርካታ ጊዜያት ከኬንያ እየተመላለሰ ስልጠና የሚሰጥ ባለሙያ የዛሬ ወር ገደማ በፖሊስ ተይዞ ከአንድ ቀን በኋላ ወደ ኬንያ እንዲባረር ተደርጓል ብሏል፡፡
ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር ሊወያዩበት እንደሚገባ ገልጿል፡፡ ጆን ኬሪ በሰሞኑ ጉብኝታቸው በኢትዮጵያ የፕሬስ አፈና መባባሱ እንዳሳሰበው በመግለፅም፣ የታሰሩት ጋዜጠኞችና ፀሐፊዎች እንዲለቀቁ ጠይቋል፡፡ ፔን የተሰኘው የፕሬስ ነፃነት ማህበርም እንዲሁ ከተመሳሳይ ጥሪ ጋር፤ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ፤ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር ሊወያበት እንደሚገባ ገልጿል፡፡ ጆን ኬሪ በሰሞኑ ጉብኝታቸው ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር የሶማሊያና የሱዳን ግጭት እንዲሁም የኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን በመጥቀስ በሰጡት የማጠቃለያ መግለጫ ላይ የጋዜጠኞቹና የፀሐፊዎቹን መታሰር አልጠቀሱም፡፡ ጉዳዩ የተነሳው ከጋዜጠኞች በቀረበ ጥያቄ ነው፡፡ ጆን ኬሪ በሰጡት ምላሽ፤ የታሰሩት ጋዜጠኞችና ፀሐፊዎች ሊለቀቁ ይገባል ብለዋል፡፡ የዩኤን ሰብዓዊ መብት ኪሚሽነር ከሰሞኑ በጋዜጠኞችና በድረገጽ ጸሃፊዎች ላይ እየተወሰደ ያለው የእስራትና የማስፈራራት እርምጃ እጅጉን እንደሚያሳስባቸው ገልጸው፣ መንግስት ሃሳባቸውን በነጻነት የመግለጽ መብታቸውን ስለተጠቀሙ በቁጥጥር ስር ያዋላቸውን ጋዜጠኞችና የድረገጽ ጸሃፊዎች እንዲፈታ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
መንግስት በስራ ላይ ያዋላቸው የጸረ ሽብር፣ የሲቪል ማህበረሰብና የመገኛኛ ብዙሃን ህጎች፣ የዜጎችን ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ፣ የመደራጀትና የመሰብሰብ መብቶች ለማፈን እየተጠቀመባቸው ነው ያሉት ፒላይ፣ ህጎቹን ከአለማቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ጋር በሚጣጣም መልኩ እንዲያሻሽልም ለኢትዮጵያ መንግስት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

Published in ዜና

43 ሚሊዮን ዶላር ፈጅቶባታል ተብሏል

          ግብጽ 43 ሚሊዮን ዶላር ያወጣችበትንና የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ የግንባታ ሂደት በአየር ላይ ሆኖ እየተከታተለ መረጃ የሚሰጣትን ወታደራዊ ሳተላይት ከሁለት ሳምንት በፊት ማምጠቋን በይፋ እንደገለፀች   አህራም ኦንላይን ዘገበ፡፡
ኢጂሳት የሚል ስያሜ የተሰጠው ሳተላይቱ፤ የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ቁመት፣ ውሃ የመያዝ አቅምና የሚለቀውን የውሃ መጠን የተመለከቱ መረጃዎችን እየተከታተለ የሚያቀርብ እንደሆነ የገለጹት የግብጽ ብሄራዊ የሪሞት ሴንሲንግና ስፔስ ሳይንስስ ባለስልጣን ምክትል ፕሬዚደንት አላ ኤልዲን ኤል ናህሪ፣ ሳተላይቱ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከሚከናወንበት አካባቢ በተጨማሪ፣ የአባይ ወንዝ በሚፈስባቸው የተለያዩ አካባቢዎች ላይ በማተኮር፣ ከፍተኛ የጥራት ደረጃ ያላቸው ጠቃሚ ፎቶግራፎችን እያነሳ እንደሚልክ  ሰሞኑን በካይሮ በተካሄደ ሴሚናር ላይ ተናግረዋል፡፡
ለሁለት ወራት ከሚቆይ የሙከራ ጊዜ በኋላ፣ በመጪው ሰኔ ወር አጋማሽ ላይ መደበኛ ስራውን ይጀምራል የተባለው  ሳተላይቱ፣ የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እየተከታተለ ለግብጽ ባለስልጣናት መረጃ ከማቀበል ባለፈ፤ የኮንጎ ወንዝን ተፋሰስ በመከተል በሚያነሳቸው ፎቶግራፎች፣ ወንዙን ከአባይ ጋር ለማገናኘት ታስቦ የተረቀቀውን የፕሮጀክት ሃሳብ ውጤታማነት በተመለከተ የራሱን ፍተሻ ያደርጋል ተብሏል፡፡ የግብጽ መንግስት ሳተላይቱ ከሚያቀርባቸው መረጃዎች የሚያገኘው ውጤት፣ ከኢትዮጵያ ጋር በግድቡ ዙሪያ የጀመረው ክርክር ተጠናክሮ እንዲገፋ እንደሚያደርገው ያምናል ያሉት አላ ኤልዲን ኤል ናህሪ፣ ግድቡን ከታለመለት የሃይል ማመንጨት ስራ ውጭ ለማዋል በኢትዮጵያ በኩል ማናቸውም አይነት እንቅስቃሴዎች ቢደረጉና ጉዳዩ ወደ አለማቀፍ ግልግል የሚያመራ ከሆነም፣ የግብጽ መንግስት ይሄንኑ የሳተላይት መረጃ ለክርክሩ የህግ ድጋፍ ለማግኘት እንደሚጠቀምበት አል አህራም ለተባለው  ጋዜጣ ተናግረዋል፡፡
አል አረቢያ ድረ-ገጽ በበኩሉ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ፣ ግብጽ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ ላይ የምታነሳቸውን ቅሬታዎች ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለማቅረብ ከወሰነች፣ ኢትዮጵያ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆኗን ባለፈው ሳምንት መናገራቸውን ዘግቧል፡፡
የግድቡ መገንባት የአባይን ወንዝ የውሃ መጠን በመቀነስ ተጎጂ ያደርገናል በሚል ተቃውሞአቸውን በተደጋጋሚ የገለፁት የግብጽ ባለስልጣናት፣ ሳተላይቱ የሚሰጣቸውን መረጃ መሰረት በማድረግ የሚደርሱበት ውጤት፣ በግድቡ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር በሚያደርጉት ክርክር ይዘውት የቆዩትን አቋም እንደሚያጠናክርላቸው ተስፋ ማድረጋቸውን ዘገባው አስረድቷል፡፡ የግብጽን ሳተላይት ማምጠቅ በተመለከተ፣ አንዳንድ ድረገጾች ቀደም ብለው መረጃ ያወጡ ቢሆንም፣ የአገሪቱ መንግስት ስለጉዳዩ ይፋዊ መግለጫ ሲሰጥና ድርጊቱን ሲያምን የአሁኑ የመጀመሪያው  ነው፡፡

Published in ዜና

           የአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ፤ ነገ በአዲስ አበባ ለሚያደርገው ‹‹የእሪታ ቀን›› የሰላማዊ ሰልፍ ቅስቀሳ በራሪ ወረቀት ሲበትኑ የነበሩ ከሰባት በላይ አመራሮችና አባላት በፖሊስ ተይዘው መታሰራቸውን ገለፀ፡፡
በሌላ በኩል፤ ሰማያዊ ፓርቲ ባለፈው እሁድ ላካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ቅስቀሳ ሲያካሂዱ የነበሩ የፓርቲውን ምክትል ሊቀመንበር አቶ ስለሺ ፈይሳ እና ምክትል የምክር ቤት ሰብሳቢው አቶ የሽዋስ አሰፋን ጨምሮ 28 አባላቱ በእስር ላይ እንደሚገኙ ገልጿል፡፡ ከሰላማዊ ሰልፉ በፊት በነበሩት ማክሰኞ፣ ረቡዕ እና ሐሙስ ቀናት በተደረጉ የቅስቀሳ ስራዎች ላይ ሳሉ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት የፓርቲው አባላት ፍ/ቤት ቀርበው የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ የተጠየቀባቸው ሲሆን “ክስ ሳይመሰረትብን ዋስትና አንጠይቅም” በማለታቸው በእስር ላይ እንደሚገኙ የፓርቲው ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
በነገው እለት አንድነት ለሚያካሂደው ሰላማዊ ሰልፍ ቅስቀሳ ሲያደርጉ የነበሩ የፓርቲው አመራሮችና አባላት ባለፈው ረቡዕና ሀሙስ የታሰሩ ሲሆን የፓርቲው ልሣን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ነብዩ ሲራክ፣ የብሄራዊ ምክር ቤት የአዲስ አበባ ዞን ሰብሳቢ አቶ ዘካርያስ የማነ ብርሃን፣  የህዝብ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ አመራር አቶ ዘላለም ደበበ እና ሌሎች አባላት በእስር ላይ እንደሚገኙ የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ሃብታሙ አያሌው ተናግረዋል፡፡
ፖሊስ የፓርቲውን አመራሮችና አባላት ያሰረው “በቤተመንግሥትና በፖሊስ ጣቢያ አልፋችኋል” በሚል ነው ብለዋል - አቶ ሀብታሙ፡፡ የአዲስ አበባ ፖሊስ በቁጥጥር ስር ባዋላቸው የአንድነት አመራሮችና አባላት ላይ ክስ እንደመሰረተባቸው የጠቆሙት አቶ ሀብታሙ፤ ትናንት በተለያዩ ፍርድ ቤቶች እንደቀረቡ ታውቋል፡

Published in ዜና

  “ሥራቸውን በገቡት ውል መሰረት ባለመስራታቸው አሰናብተናቸዋል”- ሆቴሉ
    ከአምስት ወር በፊት ስራ የጀመረው የኢሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል አራት የሴኩሪቲ ሰራተኞች፣መብታችንን በመጠየቃችን በማይመለከተን ጥፋት ወንጅሎ ያለማስጠንቀቂያ ከስራችን አባርሮናል ሲሉ በሆቴሉ ላይ ቅሬታቸውን አቀረቡ፡፡ የሆቴሉ የሰው ሃይል አስተዳደር አቶ አሰፋ በየነ በበኩላቸው፤ሰራተኞቹ የተባረሩት የተሰጣቸውን ሃላፊነትና ተግባር ወደጐን በመተው በሆቴሉ ላይ ችግር በመፍጠራቸው ነው ብለዋል፡፡ እንደማንኛውም አመልካች ተወዳድሮና መስፈርቱን አሟልቶ በሴኩሪቲ ክፍል መቀጠሩን የገለፀው አቶ ሃዲስ በሪሁን፤ አማርኛህ ለሆቴሉ አይመጥንም፣ ሴት ፈትሸሃል፣ እንግዳ አቆላምጠህ ጠርተሃልና ሌሎች   የማይመስሉ ሰበቦችን በመደርደር አስተዳደሩ ከስራው እንዳሰናበተው ተናግሯል፡፡
“የሆቴሉ ስራ አስኪያጅ ፕሮፌሰር አብዱል ሰላም ሲዮ ባሬንቶ፤ ከምሁር የማይጠበቅ ፀያፍ ንግግር ተናግረውኛል፣ የጓደኛዬን ሚስት አቆላምጬ በመጥራቴ “እሱ እስኪለቃት እየጠበቅህ ነው” በማለት ክብሬን የሚነካ ንግግር ተናግረውኛል፣ ለዚህም ምስክር አለኝ” ሲል ምሬቱን ገልጿል - አቶ ሀዲስ፡፡ “ሆቴሉ እንደማንኛውም ሰራተኛ ውል ያስገባን በቀን ለስምንት ሰዓት እንድንሰራ ቢሆንም እስከ 14 እና 16 ሰዓታት ያለ ትርፍ ሰዓት ክፍያ ተገደን ሰርተናል” ያሉት ሰራተኞቹ፤ የህክምና ኢንሹራንስ ቢኖረንም መድሀኒት የምንገዛው በግላችን ነው፣ ከተቀጠርንበት የስራ መደብ ውጭ የማይመለከተንን ስራ ሁሉ እንሰራለን፤ በአጠቃላይ ከፍተኛ በደል ደርሶብናል ብለዋል፡፡ “ከዚህ በፊት ሆቴሉ በርካታ ሰራተኞችን በግፍ አባርሯል” የሚሉት ሰራተኞቹ፤አሁንም ሊያባርራቸው ያዘጋጃቸው እንዳሉ መረጃ አለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ቀደም ሲል በትልልቅ ሆቴሎች ውስጥ በመስራት ልምድ እንዳካበተ የሚናገረው ሌላው ተሰናባች ሳሙኤል ደመመው፤ “የሴኩሪቲ ሰራተኞችን የፍተሻ ብቃት ለማረጋገጥ አንዳንድ ጊዜ ፈንጂና ቦንብን ጨምሮ መሳሪያ ታጥቆ የሚገባ እንግዳ ይላካል፣ ያንን በብቃት ፈትሾ ላገኘ የምስጋና ደብዳቤ ይሰጣል፣ በኢሊሊ ኢንተርናሽናል ይህን መሰል በርካታ የብቃት ማረጋገጫዎችን ስናልፍ እናመሰግናለን እንኳን አልተባልንም፣ ከስራ ለማባረር ግን በርካታ የማይመለከተኝን ታፔላ ለጥፈውብኛል” ሲል አማርሯል፡፡ ዋና ሥራ አስኪያጁ “ቡልሺት፣ ጋዴም” የሚሉ ስድቦችን ሰድበውን ሲያበቁ፣ “የትም ቦታ ብትሄዱ ምንም አታመጡም” በማለት በአገራችን እንደ ሁለተኛ ዜጋ ተቆጥረናል ብለዋል - ሠራተኞቹ፡፡
“በስራችን ተግተን ብንሰራም ደሞዛችን በጣም አነስተኛ ነው፣ ሰርቪስ ቻርጅ የለውም፣ የሚቀርብልን ምግብ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፣ የብሔር ወገንተኝነት የተንሰራፋበት ድርጅት ነው” ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ችግሮቹ እንዲስተካከሉ ፊርማ አሰባስበን ለሰው ሃይል አስተዳደር በማስገባታችን “ሰራተኛ አሳመፃችሁ” ተብለን ከሥራ ተፈናቅለናል ብለዋል፡፡
የሆቴሉ ስራ አስኪያጅ ፕ/ር አብዱልሰላም ሲዮ ባሬንቶ፣ በመምህርነት በተለያዩ የአለም አገራት ለ37 ዓመታት ቢሰሩም ስለ ሆቴል ማኔጅመንት የሚያውቁት ነገር ስለሌለ ስራውን እያበላሹ ነው ሲሉም ሰራተኞቹ ትችት ሰንዝረዋል፡፡ የሰራተኞቹን ቅሬታ በተመለከተ ያነጋገርናቸው የሆቴሉ ዋና ስራ አስኪያጅ ፕሮፌሰር አብዱልሰላም ሲዮ ባሬንቶ በበኩላቸው፤ በስነ-ምግባር ጉድለት፣ ኃላፊነትን በአግባቡ ባለመወጣት እና መሰል ችግሮች ሰራተኞች መሰናበታቸውን እንደሰሙና ገና ሪፖርት አለማንበባቸውን ጠቁመው፣ “በሰራተኞቹና በእኔ መካከል ሌሎች በርካታ ማናጀሮች በመኖራቸው የትኞቹ እንደተሰናበቱ አላወቅሁም” በማለት ጉዳዩ  በቀጥታ የሚመለከተው የሰው ሀይል አስተዳደሩን እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
የሆቴሉ የሰው ኃይል አስተዳደር አቶ አሰፋ በየነን በስልክ አግኝተን በሰጡን ምላሽ፤ ሆቴሉ አለም አቀፍ ሆቴል እንደመሆኑ በርካታ አለም አቀፍ እንግዶች እንደሚያርፉበት ጠቁመው፣ ከዚህ አንፃር የሴኩሪቲ  ስራ ከፍተኛ ጥንቃቄና ንቃት የሚጠይቅ ቢሆንም ሰራተኞቹ በአግባቡ ኃላፊነታቸውን ባለመወጣታቸው መሰናበታቸውን ተናግረዋል፡፡
“ስንብቱም የተፈፀመው በገባነው ውል መሰረት ነው፤ ከቃል ማስጠንቀቂያ እስከ ደሞዝ ቅጣት ደርሰናል” ያሉት አቶ አሰፉ፤ ከሴኩሪቲ ሃላፊው በደረሰን መረጃ ጥፋታቸውን ባለማረማቸውና ባለማስተካከላቸው ተሰናብተዋል ብለዋል፡፡ የጥቅማጥቅም ጥያቄን በተመለከተም ሲናገሩ፤እንደማንኛውም ሰራተኛ ሰርቪስ ቻርጅ ይከፈላቸዋል ያሉ ሲሆን ህክምናን በተመለከተም ለዓለም ከፍተኛ ክሊኒክ ጋር በገቡት ውል መሰረት፤ሰራተኞች በክሊኒኩ አስፈላጊውን ህክምና እንደሚያገኙ ተናግረዋል፡፡ የብሄር ወገንተኝነት የተባለው ሃሰት መሆኑን የገለፁት አቶ አሰፋ፤በሆቴሉ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ሀዲያ፣ ትግሬ፣ ወላይታ እና የበርካታ ብሄር ተወላጆች ተቀጥረው እንደሚሰሩ ጠቁመው “እናንተም ጋ ለአቤቱታ ከመጡት ውስጥ አማራም ትግሬም ኦሮሞም አሉበት” ብለዋል፡፡
የትርፍ ሰዓት ክፍያን በተመለከተ ሰራተኞቹ ቀደም ሲል ይከፈላቸው እንደነበር ጠቁመው ሆቴሉ በትክክል ተከፍቶ ስራ ከጀመረ በኋላ ግን በርካታ የሰው ኃይል በመቅጠርና በሶስት ሽፍት በመደልደል ሁሉም ሰው በቀን ስምንት ሰዓት መስራት እንደጀመረ ተናግረዋል፡፡
ፕሮፌሰሩ ስነ-ምግባር ይጎድላቸዋል፣ ከሆቴል ጋር የተገናኘ ሙያ የላቸውም በሚል የቀረበው ትችት ተቀባይነት እንደሌለው ሲያስረዱም “ዋና ስራ አስኪያጁ በአሜሪካ አገር ለ42 ዓመት ሲኖሩ ትምህርታቸው ሆቴል ስራ ላይ ነው ያተኮረው” ያሉት የሰው ኃይል አስተዳደሩ፤ በሆቴል ሙያ ዙሪያ ከፍተኛ ስልጠና እንደሚሰጡና በሆቴሉ ባለአደራ ቦርድ ብቃታቸው ታምኖበት መመረጣቸውን ተናግረዋል፡፡ አንድ ሰራተኛ በተሰማራበት ሙያ ላይ የሚቀመጡ መስፈርቶችና ገደቦች እንዳሉ የተናገሩት አስተዳደሩ፤ “የሆቴሉ ማናጀር የሴኩሪቲ ሰራተኛው አንዲትን እንግዳ አቅፎ ሲስም አግባብ አለመሆኑን በመናገራቸው ስማቸውን ለማጥፋት መሞከር ትክክል አይደለም፣ ኃላፊነታቸውን ባለመወጣታቸው በተወሰደው እርምጃ ገና ስራ ከጀመረ አምስት ወር ያልሞላውን ሆቴል ስም ለማጥፋት መሯሯጥ አግባብ አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ሰራተኞችን በግፍ ያባርራል፤ ሊያባርርም ተዘጋጅቷል መባሉም ከእውነት የራቀ ነው ሲሉ አቶ አሰፋ አስተባብለዋል፡፡
በሌላ በኩል የሸራተን አዲስ መሠረታዊ የሠራተኞች ማህበር 4ኛ አመት የምስረታ በአሉን ባለፈው ማክሰኞ በሆቴሉ ላሊበላ አዳራሽ የማህበሩ አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተከብሯል፡፡
የማህበሩ ሊቀመንበር አቶ ዳዊት ሣሙኤል ባደረጉት ንግግር፤ከዚህ ቀደም የሆቴሉ ሠራተኞች በአመት ለ27 ቀናት ያለ ክፍያ ማሠራትን ጨምሮ የተለያዩ በደሎች በማኔጅመንቱ ይፈፀምባቸው እንደነበር አስታውሰው፣ ከማህበሩ ምስረታ በኋላ ግን በሂደት ማኔጅመንቱ እና ማህበሩ እየተነጋገሩ የሠራተኛው ጥያቄዎች እየተመለሱ ነው ብለዋል፡፡ አሁንም በርካታ ያልተቀረፉ ችግሮች መኖራቸውን የጠቆሙት ሊቀመንበሩ፤ የፍርድ ቤት ውሣኔን የሚጠብቁ ጉዳዮችም እንዳሉ አመልክተዋል፡፡
በበአሉ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌደሬሽን (ኢሠማኮ) ተወካይ አቶ ታመነ መኮንን ባደረጉት ንግግር፤ ሠራተኛው መብቱን ለማስከበር በማህበር መደራጀት ጠቀሜታ እንዳለው አሳስበው፣ የሸራተን አዲስ ሆቴል ሠራተኞች ማህበር ለአባላቱ መብት መከበር እያደረገ ያለው ትግል በአርአያነቱ የሚጠቀስ ነው ብለዋል፡፡   

Published in ዜና

*ከ2500 በላይ ህፃናት ይሳተፋሉ
የፊታችን አርብ የሚከበረውን “የአውሮፓ ቀን” ምክንያት በማድረግ የህፃናት የሩጫ ውድድር ነገ በጃንሜዳ ይካሄዳል፡፡ የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ ልዑክ ጽ/ቤት ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ባዘጋጀው በዚህ ውድድር፤ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከሚገኙ የአንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች የተውጣጡ ከ2500 በላይ እድሜአቸው ከ14 አመት በታች የሆኑ ህፃናት ተካፋይ ይሆናሉ፡፡
ለዘጠነኛ ጊዜ በሚካሄደው በዚህ ውድድር ተካፋይ የሚሆኑት ህፃናት፤ በአራት የእድሜ ክልል ተመድበው ከአንድ እስከ ሁለት ኪሎሜትር ርቀት የሚሸፍን የሩጫ ውድድር ያካሂዳሉ፡፡ ከዚህ ውድድር ቀደም ብሎ በአለም አቀፍ ት/ቤት ህፃናት ተማሪዎች መካከል የሁለት ኪሎ ሜትር የዱላ ቅብብል ውድድር ይካሄዳል፡፡
የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ ልዑክ ጽ/ቤት ይህን የህፃናት የሩጫ ውድድር የአውሮፓ ቀንን ምክንያት በማድረግ በየአመቱ የሚያዘጋጀው፤ ስፖርት ለአንድ ሀገር እድገት የሚያበረክተውን ከፍተኛ ጠቀሜታ ከግምት ውስጥ በማስገባትና ኢትዮጵያ በአለም አቀፉ መድረክ ወደር የለሽ ክብርና ዝና በተጐናፀፈችበት የአትሌቲክስ ስፖርት ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የምታደርገውን ጥረት በመደገፍ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት መሆኑን የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ ልዑክ ጽ/ቤት የፕሬስና ኢንፎርሜሽን ኦፊሰር አቶ ሰሎሞን ከበደ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡

Published in ዜና
Page 21 of 21