እስረኞች፤ ድብደባና ግርፋት ደርሶብናል አሉ

         ከአለማቀፍ የመብት ተሟጋች ተቋም ጋር በገንዘብና በሃሳብ ተደራጅተው በኢንተርኔት አገሪቱን ለማሸበር አሲረዋል በሚል የታሰሩት 9 ጋዜጠኞችና የ“ዞን 9” ፀሐፊዎች ላይ ምርመራ እንዳልጨረሰ በመግለጽ ተጨማሪ ጊዜ እንዲፈቀድለት ፖሊስ የጠየቀ ሲሆን፤ ፍ/ቤት የ10 ቀን ቀጠሮ ሰጠ፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት ተጠርጣሪዎች ሀገሪቱን ለማሸበር በኢንተርኔት ማህበራዊ ሚዲያዎች አሲረዋል ያለው ፖሊስ፤ ሰሞኑን ተጠርጣሪዎቹ ፍ/ቤት ሲቀርቡ፣ የተያዙት በማህበራዊ ድረገፆች ላይ በፃፉት ሳይሆን ከውጭ አሸባሪ ኃይሎች ጋር በመደራጀት፣ አገሪቱን ከቀጣዩ ምርጫ በፊት ለማሸበር እና የሽብር ሴራውንም ለመምራት ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸው ነው ማለቱን የተጠርጣሪዎቹ ጠበቃ አቶ አመሀ መኮንን ተናግረዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ መንግስትን ከምርጫው በፊት ለመጣል፣ ከ5 ጊዜ በላይ እንደ ኬንያና ስውዲን ባሉ አገራት ስልጠና መውሰዳቸውን ፖሊስ ለፍ/ቤቱ ማስረዳቱንም ጠበቃው አክለው ገልፀዋል፡፡ በሶስት መዝገብ ተከፋፍለው በአራዳ ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት ጉዳያቸው የሚታየው ጋዜጠኞችና ፀሃፊዎች፤ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸው ለባለፈው ረቡዕ እና ሀሙስ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ መቀጠሩ ይታወሳል፡፡ ረቡዕ ዕለት ከቀኑ ስምንት ሰዓት ጀምሮ ኤዶም ካሳዬ፣ ናትናኤል ፈለቀና አጥናፍ ብርሃነ ችሎት ቀርበው ጉዳያቸው የታየ ሲሆን በመቀጠል ተስፋዓለም ወ/የስ፣ አስማማው ሃ/ጊዮርጊስ እና ዘላለም ክብረት ችሎት ቀርበዋል፡፡ ጉዳያቸው በዝግ ችሎታ የታየ በመሆኑ ቤተሰብ፣ እንዲሁም የውጭና የአገር ውስጥ ጋዜጠኞች የፍርድ ቤት ሂደቱን መከታተል አልቻሉም፡፡

የተጠርጣሪዎቹ ጠበቃ አቶ አመሀ መኮንን፤ ከችሎት መጠናቀቅ በኋላ ለጋዜጠኞችና ለተጠርጣሪ ቤተሰቦች በሰጡት ማብራሪያ፤ ተጠርጣሪዎቹ መጀመሪያ ከተጠረጠሩበት ጉዳይ በተለየ በውጭ ከሚገኙ አሸባሪ ሃይሎች ጋር በመደራጀት፣ እንደ ኬኒያና ስዊድን ባሉ አገሮች ከአምስት ጊዜ በላይ ስልጠና በመውሰድና ገንዘብ በመቀበል፣ ከመጪው ዓመት ምርጫ በፊት አገሪቱን ለማሸበርና የሽብር ሴራውን ለመምራትም ጭምር ሲንቀሳቀሱ እንደደረሰባቸው ፖሊስ ለፍ/ቤቱ ማስረዳቱን ገልፀዋል፡፡ ከውጭ አሸባሪ ሀይሎች በተቀበሉት ገንዘብ፣ ላፕቶፕና ኮምፒዩተር እንደገዙም ፖሊስ ለፍ/ቤቱ ማስረዳቱን የተጠርጣሪዎቹ ጠበቃ ገልፀው፤ “ፖሊስ የተጠርጣሪዎቹን ጉዳይ ከሽብርተኝነት ጋር አያይዞታል” ብለዋል፡፡

ደንበኞቻቸው የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው መጠየቃቸውን ያወሱት ጠበቃው፤ ፖሊስ ስድስት የተለያዩ ምክንያቶችን በመጥቀስ፣ የዋስትና መብታቸው እንዳይከበር መሟገቱን ገልፀዋል፡፡ ፖሊስ የዋስትና መብታቸው ቢከበር ይጐዳኛል ካለባቸው ምክንያቶች ውስጥ ተጨማሪ ግብረ አበሮች ስላሏቸው ቢለቀቁ እነሱን ያስመልጡብኛል፣ ከውጭ አሸባሪ ሀይሎች ገንዘብ ተቀብለው የገዟቸውን ላፕቶፖችና ኮምፒዩተሮች ገና አልያዝኩም፣ ተጠርጣሪዎቹ የተገኙባቸው ሰነዶች በእንግሊዝኛ የተፃፉ በመሆናቸው አስተረጉማለሁ፣ ተጨማሪ ሰነዶችን ሊያሸሹብኝ ይችላሉ፣ ምስክር ገና አላሰማሁም እና የቴክኒክ ምርመራ አልጨረስኩም በማለት ለፍርድ ቤቱ ማስረዳቱን የተናገሩት አቶ አመሀ፤ የዋስትና መብታቸው አይከበር የሚለው የፖሊስ ጥያቄ በፍ/ቤቱ ተቀባይነት ማግኘቱን ተናግረዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ፤ በቤተሰብና በወዳጅ ዘመድ እንዲጐበኙ ፍ/ቤቱን መጠየቃቸውን የተናገሩት ጠበቃው፤ ከሐሙስ እለት ጀምሮ በወዳጅ ዘመድ እንዲጐበኙ መፈቀዱን ተናግረዋል፡፡ ከትናንት በስቲያ ፍ/ቤት የቀረቡት እነ ማህሌት ፋንታሁን፣ አቤል ዋበላና በፍቃዱ ሀይሉም የተጠረጠሩበት ጉዳይ ረቡዕ እለት ከቀረቡት ከእነ ኤዶም ካሣዬ ጋር ተመሳሳይ መሆኑን አቶ አመሀ መኮንን ገልፀዋል፡፡ በሀሙሱ ችሎት ተጠርጣሪዎቹ በብሎግ፣ በፌስቡክና በቲዊተር ላይ ባሰፈሩት ፅሁፍ ተጠርጥረው አለመያዛቸውን ፖሊስ መግለፁን ጠበቃው ተናግረዋል፡፡

ረቡዕ ዕለት የተጠርጣሪዎቹ ጉዳይ የታየው በዝግ ችሎት ቢሆንም በሀሙሱ ችሎት የሶስቱ ተጠርጣሪ አንድ አንድ የቤተሰብ አባላት ወደ ችሎቱ እንዲገቡ ተፈቅዶላቸዋል፡፡ “ችሎቱ በዝግ እንዲሆን ተፈልጐ ሳይሆን ፍርድ ቤቱ የሚይዘው የሰው ብዛት አነስተኛ በመሆኑ ነው” ያሉት አቶ አመሀ፤ ባለችው ጠባብ ቦታ ቅድሚያ ለማን እንስጥ በሚል ስንነጋገር፣ ለቤተሰቦች በመባሉ፣ አንድ አንድ የቤተሰብ አባላት እንዲገቡ ተፈቅዷል፤ ተጨማሪ ማን ይግባላችሁ ተብለው የተጠየቁት ተጠርጣሪዎቹ፤ “ለጊዜው በቂ ነው” በማለት ምላሽ እንደሰጡ ጠበቃው ተናግረዋል፡፡ ከሶስቱ ተጠርጣሪዎች ሁለቱ አቤል ዋበላና በፍቃዱ ሀይሉ በእስር ቤት የሰብአዊ መብት ጥሰት እንደደረሰባቸው ለፍ/ቤቱ መናገራቸውን ያወሱት ጠበቃው፤ በደረሰባቸው ድብደባና ግርፋትም ለጉዳት መዳረጋቸውን ጠቁመው፤ የሚመለከተው አካል የሰብአዊ መብት ጥሰቱን እንዲያስቆምላቸው መጠየቃቸውን ገልፀዋል፡፡

በደንበኞቻቸው ላይ የሚፈፀመው የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዲቆም ከፖሊስ ጋር መነጋገራቸውንም ጠበቃው አክለው ተናግረዋል፡፡ ፖሊስ የጠቀሰው የሰነድ ምርመራና ማስተርጐም እንዲሁም የቴክኒክ ምርመራ ሂደት ደንበኞቻቸውን በእስር የሚያስቆይ ስላልሆነ የዋስትና መብታቸው እንዲከበር፣ ካልሆነም አጭር የጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጥ ፍ/ቤቱን መጠየቃቸውን ያወሱት ጠበቃው፤ እነ ኤዶም፣ ናትናኤል፣ አጥናፍ እንዲሁም ተስፋለም፣ አስማማውና ዘላለም ለግንቦት ዘጠኝ ሲቀጠሩ፤ ማህሌት፣ አቤልና በፍቃዱ ለግንቦት 10 ተቀጥረዋል ብለዋል፡፡ ማህሌት፣ አቤልና በፍቃዱ ከፍርድ ቤት ሲወጡ ፉጨት፣ ጭብጨባና የማበረታቻ ጩኸት ውጭ ከተሰበሰቡ ቤተሰቦችና ወዳጆች የተስተጋባ ሲሆን ጠበቃው ጩኸትና ጭብጨባው ሌሎች ችሎቶችን እየረበሸ ነው በሚል ከፍ/ቤት ማስጠንቀቂያ እንደደረሳቸው ገልፀው፤ “ጩኸትና ጭብጨባው ደንበኞቼን ስለሚጐዳ እንዳይደገም” በማለት ለቤተሰብና ወዳጅ ዘመድ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡

በሌላ በኩል፤ በረቡዕ ዕለት ችሎት ከሌሎች ጓደኞቹና ተጠርጣሪ ቤተሰቦች ጋር የጓደኞቹን ጉዳይ ውጭ ሆኖ ሲከታተል የነበረው የ“አዲስ ስታንዳርድ” መጽሔት የቀድሞ አምደኛ ኪያ ፀጋዬ፤ ተጠርጣሪዎቹ ከችሎት ሲወጡ ባልታወቀ ምክንያት ፖሊስ እየደበደበና እየተጎተተ ከታሳሪዎቹ ጋር የወሰደው ሲሆን ሃሙስ እለት ማምሻውን መለቀቁን ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ከአንድ ቀን እስር በኋላ የተለቀቀው ኪያ ፀጋዬ በምን ጉዳይ እንደተያዘ ጠይቀነው “ወደ ማዕከላዊ የተወሰድኩት ፎቶ አነሳህ ተብዬ ነው” ብሏል፡፡ “ፎቶ ማንሳት በወቅቱ አልተከለከለም፤ ፈረንጆችም ሲያነሱ ነበር፤ ፎቶ ያነሳሁትም ፍ/ቤት ውስጥ ሳይሆን ፍ/ቤት ግቢ ውስጥ ነው” ያለው ኪያ፤ ፎቶ ያነሳሁት አንዳንድ ኮመንተሪዎችን ስፅፍ ፎቶ ለመጠቀምና ለማስታወሻም ጭምር ነው ሲል ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡ ማእከላዊ ከተወሰደ በኋላ ለምን ፎቶ አነሳህ፣ ፎቶ እንድታነሳ የቀጠረህ አካል ማን ነው፣ ለማን ነው የምትሰራውና መሰል ምርመራዎች እንደተደረጉበት ጠቁሞ ባለሙያ እንደሆነና፣ ፎቶውን ያነሳው ለማስታወሻ መሆኑን ለመርማሪዎቹ ካስረዳ በኋላ በአይፎን ስልኩ ያነሳቸው ፎቶዎች ተሰርዘው፣ በነፃ መለቀቁን ለአዲስ አድማስ ተናግሯል፡፡

Published in ዜና

በትግራይ ክልል ዓረናን ትደግፋላችሁ የተባሉ አራት ባለሀብቶች፣ ዛቻና ማስፈራሪያ እንደደረሰባቸው ምንጮች ሲገልፁ ፓርቲው በበኩሉ፤ ዛቻውና ማስፈራሪያው እውነት መሆኑን ጠቁሞ የአረና ደጋፊዎች ግን ሁለቱ ባለሃብቶች ብቻ ናቸው ብሏል፡፡ በመጪው ምርጫ በክልሉ ዋና የህወሐት ተፎካካሪ ሆኖ ለመወዳደር ያቀደው ዓረና፤ በየከተሞቹ ህዝባዊ ስብሰባ በመጥራት ፕሮግራሙን እያስተዋወቀ እንደሚገኝ የፓርቲው ተወካይ አቶ አብርሃ ደስታ የጠቆሙ ሲሆን የክልሉ ባለሥልጣናትና የደህንነት ሃላፊዎች፣ የፓርቲው ደጋፊ ናቸው በተባሉ ባለሃብቶች ላይ ዛቻና ማስፈራሪያ እያደረሱባቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ባለሃብቶቹ በሚደርስባቸው ማስፈራሪያ የተነሳ ለራሳቸውና ለቢዝነሳቸው ሲሉ ድጋፍ ማድረጋቸውን ሊያቋርጡ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳደረባቸውም ተወካዩ ገልፀዋል፡፡ ከክልሉ ባለሥልጣናት ዛቻና ማስፈራሪያ ደርሶባቸዋል የተባሉትን ባለሃብቶች፣በስልክ ብናገኛቸውም “ለደህንነታችን እንሰጋለን” በሚል ምንም ዓይነት አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡ ዓረና በሚቀጥለው ሳምንት አርብ፣ በሀውዜን ከተማ የፓርቲውን ፕሮግራም ለማስተዋወቅ፣ ህዝባዊ ስብሰባ የጠራ ሲሆን በቀጣይም በአክሱም ተመሳሳይ ስብሰባ እንደሚጠራ አቶ አብርሃ ገልፀዋል፡፡

Published in ዜና

         የኢትዮጵያ አየር መንገድና የቱር ኦፕሬተርስ አሶስዬሽን የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ቱሪስቶችን ቁጥር ለመጨመር፣ በትራንስፖርትና በአገልግሎት ክፍያ ዋጋ ላይ ቅናሽ ማድረጋቸውን አስታወቁ፡፡ የሆቴሎች ዋጋም ይቀንሳል ተብሏል፡፡ በቅርቡ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድና አገልግሎት ሰጪ የሆነው የአስጐብኚ ድርጅቶች ማኅበር (ቱር ኦፕሬተርስ አሶስዬሽን) ከትናንት በስቲያ በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ ኢትዮጵያ በርካታ የቱሪስት መዳረሻ ባለቤት ብትሆንም፣ የቱሪስቶች ፍሰት ከቁጥር የማይገባ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በውጭ አገራት ያሉ የተፎካካሪ አገራት የቱሪስት ወኪሎች “ኢትዮጵያን ለመጐብኘት የትራንስፖርትና የሰርቪስ ዋጋ ውድ ነው፣ የአገልግሎት አሰጣጡ (የሆቴሎች ንፅህና፣ መስተንግዶ) ጥራት ዝቅተኛ ነው፤….” በማለት የሚያሰራጩትን የአገሪቱን ገጽታ አፍራሽ ፕሮፓጋንዳ ለማክሸፍ፣ አዲስ ስትራቴጂ ቀርፀው መንቀሳቀስ መጀመራቸውን ድርጅቶቹ ተናግረዋል፡፡ በዚሁ መሠረት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቱሪስቶችን ቁጥር ለማብዛት በትራንስፖርት ክፍያ ላይ 40 በመቶ ቅናሽ ማድረጉን የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገ/ማርያም የገለጹ ሲሆን፣ የቱር ኦፕሬተሮች አሶስዬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ፍፁም ገዛኸኝ በበኩላቸው፤ አስጐብኚ ድርጅቶች ከሚያስከፍሉት የአገልግሎት ዋጋ ላይ 20 በመቶ እንደሚቀንሱ አስታውቀዋል፡፡

የሆቴሎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አገር ውስጥ ባለመኖራቸው ምን ያህል እንደሚቀንሱ አልታወቀም፡፡ አዲሱ ስትራቴጂ የኢትዮጵያ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ የቱሪስት መስህቦች አውቆ መለየትና ለቱሪስቶች ማስተዋወቅ ነው ያሉት የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰለሞን ታደሰ፣ ለቱሪስት መዳረሻዎቹ አስፈላጊ መሠረተ ልማት (የአየርና የየብስ ትራንስፖርት፣ የንፁህ ውሃና የመብራት) አገልግሎት ማሟላት በቱሪስት መዳረሻዎቹ አካባቢ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ንፅህናው የተሟላ የመኝታ፣ የምግብ፣ አስተማማኝ ጥበቃና የደህንነት አገልግሎት በመስጠት፣ የኢትዮጵያ እምቅ ተፈጥሮዊና ታሪካዊ መስህቦች ለዓለም ማስተዋወቅ፣ የቱሪስቶችን ቁጥር ማብዛትና ከቱሪዝም ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ ማሳደግ የስትራቴጂው ግብ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ ቀደም ሲል በረሃብ፣ ድርቅና ጦርነት የምትታወቀው ኢትዮጵያ፤ ባለፉት 20 ዓመታት ባሳየችው የልማት እንቅስቃሴ በዓለም አቀፍ ደረጃ ገጽታዋ እየተለወጠ ነው ያሉት አቶ ተወልደ፤ ሚዲያውና በዘርፉ የተሰማራን ሁሉ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም፣ ዓለም አቀፍ ደረጃን ያሟላ አገልግሎት በመስጠት፣ ቱሪስቶችን ለመሳብ እንረባረብ ብለዋል፡፡

የምሥራቅ አፍሪካ አገሮችን (ኬንያ፣ ዩጋንዳ፣ ታንዛንያ) የሚጐበኙ ቱሪስቶች ቁጥር በርካታ እንደሆነ የገለፁት አቶ ተወልደ፤ ለምሳሌ በዓመት ኬንያን የሚጐበኙ ቱሪስቶች ቁጥር ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ሲሆን ኢትዮጵያን የሚጎበኙት ቱሪስቶች ከግማሽ ሚሊዮን በታች እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓለም ታዋቂና የአፍሪካ መዳረሻውም ብዙ ስለሆነ፣ ቱሪስቶች ወደ ምስራቅ አፍሪካ አገራት የሚጓዙት በእኛ አውሮፕላን ነው፡፡ በአዲሱ ስትራቴጂ ዋጋችን ተመጣጣኝና ተወዳዳሪ ስለሚያደርገን፣ የምንሰጠውም አገልግሎት ዓለም አቀፍ ደረጃውን የሚያሟላ ስለሚሆን ብዙ ቱሪስቶች ወደ አገራችን ይመጣሉ ብለዋል፡፡ የቱሪስት መስህቦቻችንን ማልማትና ማስተዋወቅ/ በቅርቡ የተቋቋሙት የኢትዮጵያ ቱሪዝም ቦርድና ኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ዋነኛ ተግባር ናቸው ያሉት አቶ ፍፁም፤ 80 በመቶ መስህቦቻችንን ለማልማት፣ 20 በመቶ ዳግም ለማስተዋወቅ ሥራ የተሰጠ በመሆኑ፣ የቱሪስት መዳረሻዎችን መሰረተ ልማት ማሟላት፣ ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት መስጠት፣ ማህበረሰቡን ማስተማር ሰፊ ድርሻ የተሰጠው በመሆኑ፤ የቱሪስቶች ቅሬታ ስለሚወገድ ብዙ ጎብኚ ይኖረናል ብለዋል፡፡

Published in ዜና

በፌደራል የስነምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ ከባድ የሙስና ክስ የተመሠረተባቸው የቀድሞ የገቢዎችና ጉምሩክ ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታ እና ምክትላቸው አቶ ገ/ዋህድ ወ/ጊዮርጊስን ጨምሮ በ3 መዝገቦች የተካተቱ ተከሣሾች ላቀረቡት የክስ መቃወሚያ ብይን ለመስጠት ፍ/ቤቱ በድጋሚ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ከትናንት በስቲያ ሐሙስ የዋለው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት፣ ተከሣሾች ያቀረቡት መቃወሚያ እና አቃቤ ህግ የሰጠው ምላሽ ተመርምሮ፣ ብይኑ ተዘጋጅቶ መጠናቀቁን አመልክቶ፣ በብይኑ ላይ የችሎቱ ዳኞች ለመወያያ አጭር ጊዜ ስለሚያስፈልጋቸው ተለዋጭ ቀጠሮ ለመስጠት መገደዱን አስታውቋል፡፡ በ3ቱም መዝገቦች ላይ ብይን ለመስጠትም ለግንቦት 8 ቀን 2006 ዓ.ም ለ3ኛ ጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

Published in ዜና

         የሼፎችና ባሬስታዎች ውድድር ይካሄዳል ሁለተኛው “ሆቴል ሾው ኢትዮጵያ 2006”፤ ከግንቦት 8 እስከ 10 በሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚካሄድ ኦዚ ሆስፒታሊቲ እና ቢዝነስ ግሩፕ አስታወቀ፡፡ በፕሮግራሙ ላይ የተለያዩ ዝግጅቶች የሚቀርቡ ሲሆን ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ ማሽኖችና ሶፍትዌር አቅራቢዎች፣ የሆቴል አማካሪ ድርጅቶች፣ ሆቴሎች፣ ሪዞርቶች ፣ የሆቴል እቃ አቅራቢዎችና የአስጐብኚ ድርጅቶች የሚሳተፉበት የንግድ ትርኢት እንደሚቀርብ ተጠቁሟል፡፡ የሀገሪቱን የሆቴልና ሆስፒታሊቲ ኢንዱስትሪ ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ እና ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያስችል ሲምፖዚየምም የዝግጅቱ አካል ሲሆን በሲምፖዚየሙ ላይ ከ400 በላይ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች ምክክር ያደርጉበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የሼፎችና ባሬስታዎች ውድድርም የሚካሄድ ሲሆን ውድድሩ ከጣሊያን እና ቱርክ በመጡ ዳኞች እንደሚዳኝ ተገልጿል፡፡ “ሆቴል ሾው ኢትዮጵያ 2006” በኢፌዲሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ድጋፍ እንደሚደረግለት የተገለፀ ሲሆን ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እንዲጐበኘውና በዘርፉ ያለው ግንዛቤ እንዲሰፋ መግቢያ በነፃ እንዲሆን መወሰኑ ተገልጿል፡፡ ዝግጅቱን ከ35ሺህ በላይ ሰዎች ይጐበኙታል ተብሎ እንደሚጠበቅ አዘጋጁ ኦዚ ሆስፒታሊቲ እና ቢዝነስ ግሩፕ ጠቁሟል፡ የመጀመሪያው “ሆቴል ሾው ኢትዮጵያ 2006” ከመስከረም 30 እስከ ጥቅምት 2 ቀን 2006 ዓ.ም በተባበሩት መንግስታት የስብሰባ አዳራሽ መካሄዱ የሚታወስ ሲሆን ከ7500 በላይ ሰዎች የንግድ ትርኢቱን እንደጐበኙት ታውቋል፡፡

Published in ዜና

         የአዲስ አበባና ኦሮሚያ ልዩ ዞን የጋራ ማስተር ፕላንን ጨምሮ የተለያዩ አስተዳደራዊ ጥያቄዎችን በማንሳት ተቃውሟቸውን የገለፁ የሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፤ “ጥያቄያችን አልተመለሰም” በሚል እስከ ትላንትና ድረስ በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት እና መስጊዶች እንደተጠለሉ መሆናቸውን ምንጮች ገለፁ፡፡ ተማሪዎች ከአነሷቸው ጥያቄዎች መካከል የአዲስ አበባ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የጋራ ማስተር ፕላንና በፌደራል መንግስት ከሚተዳደሩ የኦሮሚያ ከተሞች ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ይገኙበታል ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል በዘር የተቧደኑ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች የፈጠሩትን ረብሻ ተከትሎ፣ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት እንዲሁም የአገር ሽማግሌዎች ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ከተማሪዎቹ ጋር ውይይት ማካሄዳቸውን ምንጮች ገልፀዋል፡፡ የትራንስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ወርቅነህ ገበየሁ፣ የኦሮሚያ ምክትል ፕሬዚዳንት አብዱላዚዝ አህመድን ጨምሮ የሐረሪ ክልል ም/ፕሬዚዳንት አቶ ረጋሣ ከፈለ ከተማሪዎች ጋር የተወያዩ ሲሆን ጥያቄያቸውን በሰላማዊ መንገድ በተማሪዎች ጉባኤ ማቅረብ እንጂ በረብሻ መግለፅ እንደሌለባቸው ተነግሯቸዋል - ምንጮች እንደገለፁት፡፡

Published in ዜና

             ከሩብ ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ለመኪና ማቆሚያ የሚሆን ፎቅ እንደሚያስገነባ የገለፀው ኢሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል፤ በቡራዩ እና በቢሾፍቱ ሁለት ዘመናዊ ሪዞርቶችን ሊያስገነባ ነው፡፡ ባለፈው ህዳር ወር ስራ የጀመረው ኢሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል፤ አለማቀፍ ደረጃዎችን በማሟላት በሃገራችን አሉ ከሚባሉ ሆቴሎች አንዱ መሆኑን የገለፁት ስራ አስኪያጁ ፕ/ር ኤዲ ባሬንቶ፤ በግንባታ ጥበቡ በውስጣዊ ይዘቱ፣ በቴክኖሎጂዎች አጠቃቀሙና በሰው ኃይል አደረጃጀቱ እጅግ ዘመናዊ በመሆኑ የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ ድምቀት እንደሆነ ማንም ሊመሰክር ይችላል ብለዋል፡፡ በ1690 ካሬ ሜትር ለመኪኖች ማቆሚያ (ፓርኪንግ) አገልግሎት የሚሰጥ አለማቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ፎቅ በ 258 ሚሊዮን ብር እንደሚያስገነባ ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

የኢሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል ባለቤት አቶ ገምሹ በየነ፤ ዘመናዊ የመዝናኛ ስፍራዎችንና ሰፋፊ የስብሰባ አዳራሾችን ያካተተ ሪዞርት በቡራዩ እያስገነቡ ሲሆን፤ ሪዞርቱ አዲስ አበባን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ከፍታ ቦታ ላይ መሆኑን ፕ/ር ባሬንቶ ገልፀዋል፡፡ በቢሾፍቱ ባቦጋያ ሃይቅ አካባቢ እየተገነባ ያለው ሌላው ሪዞርት እጅግ ዘመናዊ መሆኑን ፕ/ር ባሬንቱ ሲያስረዱ፤ በአገሪቱ የመጀመሪያው ተጠቃሽ እንደሚሆን ጠቁመው፤ 2500 ሰው መያዝ የሚችል የስብሰባ አዳራሽ የያዘ ነው ብለዋል፡፡

በሆቴል ዘርፍ በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ሃብት ኢንቨስት ያደረጉት አቶ ገምሹ በየነ፤ በመሰረተ ልማት በተለይም በመንገድ ግንባታ ላይ የተሰማራ “ገምሹ በየነ ኮንስትራክሽን (GEBECON)” የተሰኘ ኩባንያ ባለቤት መሆናቸውን ፕ/ሩ ጠቅሰው፤ በሃገሪቱ የመሰረተ ልማት እድገትና የስራ እድል ፈጠራ ላይ የራሳቸውን አሻራ ለማሳረፍ እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡ ከ6ሺ በላይ ሰራተኞች ያሉት የኮንስትራክሽን ኩባንያው፤ በእውቅ የምህንድስና ባለሙያዎች የተደራጀ መሆኑን የገለፁት ፕ/ሩ፣ ከገነባቸው መንገዶች መካከል በትግራይ ከማሃበሬ እስከ ዲማ እና ከዲማ እስከ ፈየል ውሃ፣ በጐንደር ከአዘዞ እስከ ጎርጎራ እና የመሃል ሜዳ መንገድ ይገኙበታል፡፡ በተጨማሪም ከድሬድዋ እስከ ደወሌ እንዲሁም በሶማሌና በሃረሪ ክልል የመንገድ ግንባታዎችን ያከናወነው ኩባንያው፣ በርካታ መንገዶችን ሰርቶ እንዳስረከበ ተገልጿል፡፡

ፕ/ር ባሬንቶ ስለ አቶ ገምሹ በየነ ሲናገሩ፤ ከኢንቨስትመንት ጋር በተለይ በበጐ አድራጐትና በአገር ወዳድነታቸው የሚታወቁ ናቸው ይላሉ፡፡ በዘርና በጎሳ የማያምኑ፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ባላቸው እውቀትና ብቃት ሰርተው ኑሯቸውን እያሻሻሉ፣ ሃገራቸውንም እንዲጠቅሙ የሚጣጣሩ በመሆናቸው፣ በፈተና እና በስራ ምዘና እንጂ በዝምድና እንኳ እንደማይቀጥሩ በማየት እናደንቃቸዋለን ብለዋል፤ ፕ/ር ባሬንቶ፡፡

Published in ዜና

•    ለግንባታው 31 ሚሊዮን ዩሮ ያስፈልጋል ተብሏል
በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኘውን የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ (የቆሼ - ረጲ ቆሻሻ ማስወገጃ) ለመለወጥ የሚያስችል የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ በሰንዳፋ ሊገነባ  ሲሆን ግንባታው 31 ሚሊዮን ዩሮ እንደሚፈጅ ታውቋል፡፡
አዲሱ የቆሻሻ ማስወገጃ ሥፍራ ከአዲስ አበባ ከተማ በተጨማሪ፣ በከተማዋ ዙሪያ የሚገኙ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞችንም ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል፡፡
ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከትናንት በስቲያ በቀረበው የብድር ስምምነት ማፅደቂያ ረቂቅ አዋጅ ላይ እንደተገለፀው፤ የአዲስ አበባ ከተማን የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ዘመናዊና ተደራሽ ለማድረግና ለነዋሪው ደረጃውን የጠበቀ ቀልጣፋ የቆሻሻ አወጋገድ አገልግሎት ለመስጠት እንዲቻል ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፡፡ የከተማዋ አስተዳደር ከኦሮሚያ ክልል መስተዳድር ጋር በመመካከር፣ ለዚሁ ተግባር የሚውል ቦታ በሰንዳፋ አካባቢ እንዳዘጋጀም ተጠቁሟል፡፡
ለአዲሱ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ግንባታ፣ 31 ሚሊዮን ዩሮ የሚያስፈልግ ሲሆን 20 ሚሊዮን ዩሮ ያህሉ  ከፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ በብድር እንደተገኘ  ተገልጿል፡፡ ቀሪው ገንዘብ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚሸፈን እንደሚሆን  ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የብድር ስምምነት ማፅደቂያ ረቂቅ አዋጅ አመልክቷል፡፡

Published in ዜና

•    ድርጅታችን አሸናፊ መሆኑ ከተገለፀልን በኋላ ያለ አግባብ ውጤቱ ተሰርዟል
•    ጉዳዩን ለፀረ ሙስና አቅርቧል

የ “ታምሩ ፕሮዳክሽን” ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አርቲስት ታምሩ ብርሃኑ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ለተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎች ባወጣው ጨረታ ያለአግባብ በደል ፈጽሞብኛል ሲል ቅሬታውን ገለፀ፡፡
አርቲስቱ ትናንት ረፋድ ላይ ቦሌ በሚገኘው አምባሳደር ሆቴል በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው የቅሬታው መንስኤ ኢሬቴድ ነሐሴ ወር 2005 ዓ.ም ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎችን ለማቅረብ ፍላጐት ያላቸው ድርጅቶች እንዲወዳደሩ ባወጣው ጨረታ የተሳተፈው ድርጅቱ “ታምሩ ፕሮዳክሽን” አንደኛ መውጣቱ ከድርጅቱ የስራ ሃላፊዎች ከተገለፀለት በኋላ፣ ያለአግባብ ውጤቱ ተቀይሮ ከአሸናፊነት እንዲሰረዝ ተደርጓል፡፡
“ታምሩ ፕሮዳክሽን” አንደኛ መውጣቱ ከተገለፀለት በኋላ፣ ኢሬቴድ በጨረታ ሰነዱ ውስጥ ያልተካተተ “የመጨረሻ ዙር” የሚል ውድድር አዘጋጅቶ አንደኛ የወጣውን የታምሩ ፕሮዳክሽን ነጥብ በመሻር፣ ሚያዚያ 24 በተፃፈ ደብዳቤ ከጫወታ ውጭ እንዳደረገው የገለፀው አርቲስት ታምሩ፣ ድርጊቱ በጣም እንዳሳዘነው ጠቁሞ፣  “ከዚህ ጋር ተያይዞ የደረስብንን የሞራል የገንዘብ የጊዜና ሌሎች ኪሳራዎቻችን በህጋዊ መንገድ ለማካካስ ጥረት እናደርጋለን” ብሏል፡፡  ጉዳዩን ለኢፌዲሪ የስነ ምግባርና የፀረ - ሙስና ኮሚሽን አቅርቦ  እየታዬ መሆኑን ጠቁሞ፣ በተጨማሪም ለኢሬቴድ ዋና ዳይሬክተርና ለቦርድ ሰብሳቢው ለአቶ ሬድዋን ሁሴን አቤቱታ ማቅረቡንና ጉዳዩ ተመርምሮ በአጭር ጊዜ መፍትሔ እንደሚሰጥበት ቃል እንደገቡለት ተናግሯል፡፡ ድርጅቱ ተገቢውን መፍትሔ የማይሰጠው ከሆነ፤  ጉዳዩን ወደ ፍ/ቤት እንደሚወስደውም ገልጿል፡፡
ጉዳዩን ለማጣራት የኢሬቴድ ኮሚሽኒንግ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ለሆኑት አቶ ገብረአምላክ ተካ በተደጋጋሚ ብንደውልም ስልካቸውን ባለማንሳታቸው ምላሻቸውን ማካተት አልቻልንም፡፡ ወደ ድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅና ም/ሥራ አስኪያጅ ቢሮ ደውለን የነበረ ሲሆን ሁለቱም ስብሰባ ላይ በመሆናቸው ልታገኟቸው አትችሉም የሚል ምላሽ ከፀሐፊዋ አግኝተናል፡፡


Published in ዜና


ዳሽን ባንክ እና የአሜሪካው ኤክስፕረስ ኔትወርክ የኤቲኤም የካርድ አገልግሎት ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን በቅርቡ የአሜሪካ ኤክስፕረስ ካርድ አገልግሎት በሁሉም የዳሽን ባንክ ኤቲኤም ማሽኖች እንደሚጀምር ተገለፀ፡፡ የባንኩ የፕሮሞሽን ዋና ክፍል ኃላፊ አቶ እስጢፋኖስ በፈቃዱ፤ የኤቲኤም ማሽን የካርድ አገልግሎቶችን እየተገበረ መሆኑን አስታውሰው፤ በሃገሪቱ ብቸኛ ባንክ የሚያደርገው፤ የአሜሪካን ኤክስፕረስ ካርድ አገልግሎት፣ የሙከራ ሂደቱ እንደተጠናቀቀ በይፋ ይጀምራል ብለዋል፡ በርካታ የውጭ ሃገር ቱሪስቶች የአሜሪካን ኤክስፕረስ ካርድ ተጠቃሚ ናቸው ያሉት ኃላፊው እስከዛሬ በዚህ ካርድ በኢትዮጵያ ውስጥ ገንዘብ ማውጣት እንደማይቻል ጠቁመው፤ ዳሽን ባንክ አገልግሎቱን መጀመሩ ብቸኛው እንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ ወ/ስላሴ በስምምነት ፊርማው ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ባንካቸው በኢትዮጵያ ያለውን የልማት እንቅስቃሴ እየደገፉ መሆኑን ጠቅሰው፤ እስካሁን ካሉት የኤቲኤም ካርዶች በተጨማሪ፣ የአሜሪካን ኤክስፕረስ ካርድ አገልግሎት መጀመሩ፣ ባንኩንም ሃገሪቱንም ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል ብለዋል፡፡ ዳሽን ባንክ በኢትዮጵያ ተጠቃሽ ከሆኑ የፋይናንስ ተቋማት አንዱ ነው ያሉት የአሜሪካ ኤክስፕረስ ዋና ስራ አስፈፃሚ ፒተር ላይስ በበኩላቸው፤ ባንኩ ለደንበኞች አገልግሎት እርካታ የሚተጋ መሆኑን፣ የአሜሪካን ኤክስፕረስ ካርድ ተጠቃሚነቱ ይመሰክራል ብለዋል፡፡

Published in ዜና