በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፍልስፍና መምህር የሆኑት እና በጠንካራ ፖለቲካዊ ትችታቸዉ የሚታወቁት ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ፤ የመኢአድ አባል በነበሩት በእነ አቶ ማሙሸት አማረ “የብአዴን አባል ነው፤ ለመኢአድ መሪነት ታጭቷል፤ መባላቸው ሃሰትና ተራ አሉባልታ መሆኑን ለአዲስ አድማስ ገለጹ፡፡ ዶ/ር ዳኛቸው እንደተናገሩት ፤ ከሶሥት ወራት በፊት ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያምና እሳቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቢያንስ በሚግባቡባቸው ጉዳዮች ላይ አብረው እንዲሠሩ ለማግባባት ሽምግልና መጀመራቸውን ጠቁመው ሆኖም ሽምግልናው አለመሣካቱን ይናገራሉ፡፡ “በዚህ ሽምግልና ወቅት ኢ/ር ሀይሉ ሻውል ለእኔና ለዶ/ር ያዕቆብ የአባልነት ፎርም እንድንሞላ ሠጡን” የሚሉት ዶ/ር ዳኛቸው እርሳቸውም ሆኑ ዶ/ር ያዕቆብ ጥያቄውን አለመቀበላቸውን ይናገራሉ፡፡ “እኔ በጣም እየደከምኩ ነው፤ ፓርቲውን ለሁለተኛ ሰው ማስረከብ እፈልጋለሁ፡፡

ስለዚህ አባል ሁኑ” በማለት ኢንጂነር ሀይሉ እንደጠየቋቸው የገለፁት ዶ/ር ዳኛቸው፤ “የፓርቲው መሪ ኹኑ” የሚል ነገር ግን አልተነሳም ብለዋል፡፡ “ዶ/ር ያዕቆብ እኔ ከፓርቲ ፓርቲ መዝለል ሰልችቶኛል፤ አልፈልግም ብለው ጥያቄውን አልተቀበሉም፣ እኔም ብሆን በወቅቱ አሜሪካ ቤተሠብ ለመጠየቅ መሄድ ስለነበረብኝ እና በአካዳሚክ ነፃነቴ ላይ ተፅዕኖ ይፈጥርብኛል የሚል አቋም ስላለኝ አልተቀበልኩም” ብለዋል ዶ/ር ዳኛቸው፡፡ እነ አቶ ማሙሸት አማረ ከመኢአድ ተጣልተው ስለመውጣታቸው ከመስማት በስተቀር እንደማያውቋቸው የተናገሩት ዶ/ር ዳኛቸው፣ ስለ አባልነት ጥያቄ ሲወራ ስለነበር ከሌላ ቦታ መጥቶ መሪ ሊሆን ነው የሚል ጭንቀት ቢያድርባቸው እንደማይፈረድባቸዉ ገልፀው፣ ይሁን እንጂ ይህን ፍርሀት ለመግለፅ “ዳኛቸው የብአዴን አባል ነው” የሚል የበሬ ወለደ ፈጠራ ማውራታቸዉ እንዳሣዘናቸው ተናግረዋል፡፡ “ይህን ዘገባ ያወጣው ጋዜጣም ሆነ ጋዜጠኛው ከበሬታ የላቸውም” ያሉት ዶ/ር ዳኛቸው፤ አንድ የሙያ ስነ-ምግባር ጠብቄ እሠራለሁ የሚል የሚዲያ ተቋምም ሆነ ጋዜጠኛ የአንድ ወገን መረጃ ብቻ በመያዝ ከስም አጥፊዎች ጋር መተባበሩ እጅግ አሳዝኖኛል ብለዋል፡፡

“ኢህአዴግ ከገባ 22 አመት ሆኖታል፣ እኔም ለ11 ዓመታት እየተመላለስኩ ለሁለት ለሁለት ወራት ሳስተምር ነበር” ያሉት ዶ/ር ዳኛቸው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ሙሉ በሙሉ መኖር ከጀመሩ ስድስት ዓመት ተኩል እንደሆናቸው አስታውሠው፣ “በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ስመላለስ አንድም ቀን ዳኛቸውን በብአዴን ቢሮ ወይም ስብሠባ ላይ ዳር አይተነዋል የሚል ሠው ካለ ማስረጃ ያቅርብ” ብለዋል፡፡ ኢህአዴግ ከገባ በኋላ አስሩን ዓመታት በአሜሪካ ቦስተን ከተማ እንደኖሩ የገለፁት ዶ/ሩ በቦስተን ውስጥ ሻዕቢያ፣ ኦነግ፣ ኢህአፓና ሌሎች ፓርቲዎች ተወካይ እንዳላቸውና ብአዴን ግን ተወካይ እንደሌለው ገልፀው፣ “እነ አቶ ማሙሸት ከየት አምጥተው አወሩት” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ “በዚህ አጋጣሚ ጋዜጣውም ሆነ እነ አቶ ማሙሸት ቦስተን ደውለው እዛ ያሉትን ተወካዮች ዳኛቸው የብአዴን ተወካይ ነው ወይ ብለው ቢጠይቁ በቀላሉ መልሱን ያገኙታል፤” ብለዋል፡፡ ዶ/ር ዳኛቸው አክለውም እስከዛሬ የየትኛውም ፓርቲ አባል ሆነው እንደማያውቁ ጠቁመው የኢ/ር ሀይሉን የአባል ሁን ጥያቄ ያልተቀበሉት በአካዳሚክ ነፃነታቸው ላይ ተፅዕኖ እንዳይፈጥርባቸው ስለሚፈልጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ “እርግጥ ድሮ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እና አሜሪካም እያለሁ የተማሪ እንቅስቃሴ አባል ነበርኩኝ” ያሉት ዶ/ሩ፤ “ከዚያ ውጭ እንኳን የብአዴን የምወደው የኢህአፓም አባል አልሆንኩም” ብለዋል፡፡ “እኔ የእነ አቶ ማሙሸት ጭንቀትና ፍርሀት ይገባኛል፡፡ በለፋንበትና በደከምንበት ቤት መጥቶ መሪ ሊሆንብን ነው ብለው ቢሰጉ አይፈረድባቸውም፤” የሚሉት ዶ/ር ዳኛቸው፤ ኢ/ር ሀይሉም ቢሆኑ በሳልና የበቁ ፖለቲከኛ በመሆናቸው ያለ ፓርቲው ደንብና ሥርዓት እከሌ አስተሳሰብህና ንግግርህ ተመችቶኛልና መጥተህ የፓርቲ መሪ ሁን” የሚሉ እንዳልሆኑ በአፅንኦት ገልፀዋል፡፡ ይኹንና እነ አቶ ማሙሸት ጭንቀታቸው እንዳለ ሆኖ ገና ለገና መጥቶ የአመራር ቦታ ይይዛል በሚል የስም ማጥፋት ዘመቻ ማካሄድ ነውር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ “ይህን የስም ማጥፋት ዘመቻ በትብብር አትሞ ያወጣው ጋዜጣም ሆነ የዘገበው ጋዜጠኛ በደንብ ያውቁኛል” ያሉት ምሁሩ፣ ስልክ ቁጥራቸውንና ቢሯቸውን እያወቁ ሀሣባቸው ሳይካተትና ሚዛናዊ ሳይደረግ መፃፉ የጋዜጠኝነትን ሙያ የሚቃረን መሆኑን ገልፀዋል፡፡

“እኔ የብአዴን አባል ብሆን ኖሮ ወረቀት በታኝ ሆኜ የምቀር ይመስላችኋል” ሲሉ የሚጠይቁት ዶ/ሩ፤ በአሁኑ ሠዓት የሀይስኩል ትምህርታቸውን በወጉ ያላጠናቀቁ የብአዴን አባላት አምባሣደር ሲሆኑ እኔ ቦታ ሳይሠጠኝ ይቀር ነበርን? በማለት ዘገባውን አጣጥለዋል፡፡ አክለውም “አባል ሆኜ ድምፄ ሳይሠማ የእነ ህላዌ እና የነበረከት ስምኦን ወረቀት በታኝ ሆኜ ልቀር አልችልም” የሚሉት ዶ/ሩ ይህን ውሸት ባወሩትና ወሬውን ባተመው ጋዜጣ ከልብ እንዳዘኑ ተናግረዋል፡፡ “እኛ ሎጂክ ስናስተምር በሎጂክ አንድ ሠው ከመሬት ተነስቶ እከሌ ሠው ገድሏል ብሎ ቢያወራ ገደለ የተባለው ሠው አለመግደሉን ማረጋገጥ አይችልም” ያሉት ዶ/ር ዳኛቸው፤ ገደለ ብሎ ያወራው ሠው ግን እንዴት፣ መቼና በምን ሁኔታ እንደገደለ ማስረጃ ማቅረብ አለበት፤ የእኔንም የብአዴን አባልነት በዚህ መልኩ ሲሣተፍ፣ ስብሠባ ላይ ንግግር ሲያደርግ እንዲህ አይነት የፎቶግራፍ፣ የሠነድ፣ የቪዲዮ ማስረጃ አለን ብለው በማቅረብ ማረጋገጥ ያለባቸው እነ አቶ ማሙሸት ናቸው፡፡ የጨዋታው ኳስ ያለው በእነርሱ ሜዳ ላይ ነው” ብለዋል፡፡ በመጨረሻም “በተቃዋሚዎች የእርስ በእርስ ግጭት ተጠቃሚው ኢህአዴግ ነው” ያሉት የፍልስፍና ምሁሩ፤ ለዚህ ተጠቃሚነቱ ደግሞ የሚተጉ አካላት እንደሚያሳዝኗቸው ተናግረዋል፡፡

Published in ዜና

የአቡነ ጳውሎስን ሃውልት የማፈንዳት እቅድ እንዳለ ተነግሯቸዋል አዲስ አበባ በመምጣት ሁለት ጊዜ ስልጠና መስጠታቸውን አምነዋል በግንቦት 7 አባልነት እና ከአመራሮች ተልዕኮ በመቀበል የሚያስከትለው ጉዳት እያወቁ የፈንጂ ስልጠና ሰጥተዋል ተብሎ እስካሁን በፍርድ ቤት ካልቀረቡት አንደኛ ተከሳሽ ሻለቃ ማሞ ለማ ጋር የተከሰሱት 2ኛ ተከሳሽ አበበ ወንድማገኝ ልደታ በሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ረቡዕ ዕለት ቀርበው በሠጡት ቃል የፈንጂ ስልጠና መስጠታቸውን አመኑ፡፡ ተከሣሹ ስለፈፀሙት ድርጊት ሲያብራሩም የፈንጂ ስልጠናውን የሠጡት ከሚኖሩበት እንግሊዝ ለንደን ከተማ ለእረፍት ቤተሠባቸውን ይዘው በመጡበት አጋጣሚ መሆኑንና በዚያው ኢትዮጵያ ስትሄድ የፈንጂ ስልጠናውን ስጥ የሚል ትዕዛዝ ከሻለቃ ማሞ እንደተላለፈላቸው ገልፀዋል፡፡

ፈንጂው የሚፈነዳው ቦሌ መድሃኔአለም በሚገኘው የአቡነ ጳውሎስ ሃውልት ላይ መሆኑ እንደተነገራቸው የጠቆሙት ተከሳሹ፤ ለምንድን ነው ሃውልቱ ላይ እንዲፈነዳ የተፈለገው ብለው ሲጠይቁ የተባልከውን ዝም ብለህ ፈፅም የሚል ትዕዛዝ እንደተሰጣቸው ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። የእንግሊዝ ዜግነት እንዳላቸው በመግለፅም ወታደር የመሆን ፍላጐት ስላደረባቸው የእንግሊዝ መንግስትን በውትድርና ሰልጥነው እንዲቀጠሩ ጠይቀው እንደነበር የገለፁት ተከሳሹ፤ የእንግሊዝኛ ቋንቋቸው ደካማ በመሆኑ ተቀባይነት እንዳላገኙ፣ በዚህ መነሻነትም ለምን አላማ እንደሚሰለጥኑ ባይረዱም ይህን ፍላጐታቸው ለሻለቃ ማሞ ተናግረው እሳቸው ባመቻቹት መንገድ ወደ ኤርትራ በመግባት “ኢን” በተባለ ቦታ የፈንጂና የመሣሪያ ትምህርቶችን በኤርትራውያን አሰልጣኞች ለሦስት ሣምንታት መሰልጠናቸው ተናግረዋል፡፡ “በወቅቱ ፊልም ላይ እንደማየው አይነት ስልጠና እንዲሰጠኝ ነበር የፈለግሁት” የሚሉት ተከሳሹ፤ ነገር ግን እዚያ ከደረሱ በኋላ ከፈንጂና ከመሣሪያ ስልጠና በቀር የጠበቁትን እንዳላገኙ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡

ተከሣሹ በሰጡት የእምነት ክህደት ቃል ስልጠናውን ከመውሰዳቸው በተጨማሪ የቅንጅት አባል ባይሆኑም በተለያዩ የቅንጅት ስብሰባዎች ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ ሻለቃ ማሞ ለማም አሁን ያለው መንግስት ያለ ትግል ሊቀየር እንደማይችል ነግሮኛል ያሉት ተከሳሹ፤ በወቅቱ እሳቸውም ያስፈልጋል ብለው ማመናቸውን ተናግሯል፡፡ በተደጋጋሚ በሰዎች ግፊት በስህተት ሳላውቅ የፈፀምኩት ድርጊት ነው ሲሉ ያስረዱት ተከሳሹ፤ ቀደም ሲል በ2003 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ፒያሣ ቸርችል ጐዳና 2ኛ ፖሊስ ጣቢያ ፊትለፊት መኪና ውስጥ በገመድ የሚነሳ ፊውዝ የተባለውን ፈንጂ ማሰልጠናቸውን አምነዋል፡፡ ፖሊስ ጣቢያ በር ላይ ለማሰልጠን ለምን ፈለግህ የሚል ጥያቄ ከዳኞች የቀረበለላቸው ተከሣሹ ከእይታ ትኩረት ነፃ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡

ተከሣሹ ቃላቸውን ሲሰጡ የተልዕኮው ባለቤት ግንቦት 7 መሆኑን ያወቁት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ከመርማሪዎቹ መሆኑንም ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡ አቃቤ ህግም ተከሣሹ የፈንጂ ስልጠና መስጠታቸውን ብቻ እንዳመኑ በማስታወስ ድርጊቱን መፈፀማቸውን ሙሉ ለሙሉ ስላላመኑ ማስረጃውን ለማጠናከር እንዲረዳ ምስክሮችን አቅርቤ እንዳሰማ ይፈቀድልኝ ያለ ሲሆን ፍርድ ቤቱም ጥያቄውን ተቀብሎ ምስክሮቹን አቅርቦ እንዲያሰማ ፈቅዷል፡፡ የአቃቤ ህግ ምስክሮችም ግንቦት 26 ቀን 2005ዓ.ም እንዲሰሙ ፍርድ ቤቱ ወስኗል፡፡ ፍርድ ቤቱ ቀደም ብሎ የተከሳሽ ጠበቃ ያቀረቡአቸውን መቃወሚያዎች በከፊል ውድቅ ያደረገ ሲሆን በመቃወሚያው የህግ አንቀፁ አልተጠቀሰም የተባለውን አቃቤ ህግ አንቀፁን ጠቅሶ ክሱን እንዲያቀርብ አዟል፡፡ ቀደም ሲል በዋለው ችሎት የተከሳሽ ጠበቃ፤ ክሱ ግልጽ አይደለም በተለይም የወንጀሉን አይነት በሚገባ አይገልጽም ሲሉ ያቀረቡትን መቃወሚያ በተመለከተ ፍርድ ቤቱ የወንጀሉ አይነት በሚገባ ተጠቅሷል፤ ክሱ ግልጽ አይደለም የሚለው ማስረጃዎች ከታዩ በኋላ የሚወስን በመሆኑ ተቀባይነት አላገኘም ብሏል፡፡

Published in ዜና

የማተሚያ ማሽኑ ዋጋ 8ሺ ዶላር ነው፤ ስምንት ሺ ሽጉጦችን ሊሰሩበት ይችላሉ። ፅሁፍ የሚያትም ሳይሆን ሽጉጥ ወይም ሌላ እቃ የሚያትም ማሽን ነው - 3D printer ይሉታል። የዘንድሮ ምርጥ ፈጠራ እንደሆነ የተነገረለት “ቅርፅ አታሚ ማሽን”፣ በሚቀጥሉት አመታት ገበያውን እንደሚያጥለቀልቅ ተተንብዮለታል። ትንቢቱ ወር ሳይሞላው፤ አለምን ሲያነጋግር የሰነበተ የህትመት ውጤት ብቅ አለ - በማተሚያ ማሽን የተሰራ የመጀመሪያው ሽጉጥ። መልኩ ከዘመናዊ የቢሮ ፅሁፍ ማተሚያ ማሽን በመልክ ብዙም አይራራቅም። አሰራሩም ተመሳሳይ ነው - ከኮምፒዩተር በሚደርሰው ትዕዛዝ አትሞ ማውጣት (ፅሁፍ ሳይሆን ቅርፅ)። የመጀመሪያው የሽጉጥ እትም በዚሁ ሳምንት በአደባባይ ተሞክሮ የመጀመሪያውን ጥይት ተኩሷል። ዲፈንስ ዲስትሪቢዩተር በተባለ ኩባንያ ተሰርቶ የተሞከረው ሽጉጥ Liberator የሚል ስም ተሰጥቶታል - ነፃ አውጪ እንደማለት። ሽጉጡ ከፕላስቲክ የተሰራ ቢሆንም፣ ማንም አላናናቀውም - የመተኮስ ስራውን በአግባቡ የሚያውቅ ነውና። ፍርሃት ያደረባቸው ግን አሉ።

ብዙዎቹ የመፈተሻ መሳሪያዎች፣ ብረታማ ነገሮችን ለይተው እንዲያሳዩ የተሰሩ ናቸው። የፕላስቲክ ሽጉጥ የታጠቀ ሰው፣ የፍተሻ መሳሪያዎች ሳያግዱት ማለፍ የሚችል መሆኑ፣ አንዳንድ የአሜሪካ ህግ አውጪ ምክርቤት አባላትን አሳስቧል። የጦር መሳሪያ ቁጥጥር አከራካሪ በሆነበት ወቅት፣ የብዙዎችን ትኩረት የሳበ አዲስ አይነት ሽጉጥ መፈጠሩ፣ አጋጣሚውን አስገራሚ አድርጎታል። ደግሞም ማንም ሰው በየቤቱ ኮምፒዩተርና “ፕሪንተር”ን እየተጠቀመ ሊፈበርከው ይችላል። በእርግጥ “ማንም ሰው ይችላል” የሚለው አነጋገር የተጋነነ ነው። ከኮምፒዩተሩ ወደ ፕሪንተሩ የሚተላለፈውን ትዕዛዝ (ንድፍ) አስተካክሎና ጠንቅቆ ማወቅ ያስፈልጋል። ይህንን ደግሞ “ማንም ሰው ይችለዋል” የሚባል አይደለም። ነገር ግን፤ ብዙዎችን አላስጨነቃቸውም።

ምክንያቱም፣ የአዲሱ ሽጉጥ ንድፍ በኢንተርኔት ተሰራጭቷል። ፎርብስ መፅሄት እንደዘገበውም በጥቂት ቀናት ውስጥ ከ100 ሺ በላይ ሰዎች፣ ንድፉን ከኢንተርኔት አግኝተው የራሳቸው አድርገውታል። ደግሞም፣ ሌሎች አማራጮች አሉ። የጦር መሳሪያ ባለቤት የመሆን መብት እንዲከበር በሕገመንግስት ባወጀችው አገር ውስጥ፣ መንግስት በጦር መሳሪያ ላይ አዳዲስ የቁጥጥርና የገደብ ህጎችን ማዘጋጀቱ ያስቆጣቸው ሰዎች ብዙ አማራጮችን እየፈጠሩ ነው - ለምሳሌ፣ አንድ የዩኒቨርስቲ ተማሪ፣ የሽጉጥ ንድፍ ሰርቶ በኢንተርኔት አሰራጭቷል። ይሄኛው ሽጉጥ 400 ጥይቶችን በመተኮስ በተግባር የተሞከረ ሲሆን፣ ከ400 ሺ በላይ ሰዎች የሽጉጡን ንድፍ ከኢንተርኔት ወስደዋል። የአሜሪካ ነገር፣ አጃኢብ ነው።

Published in ዜና

ወዳጆቼ --- በቀጥታ ወደ ቁምነገሩ ከመግባታችን በፊት በቀልድ ዘና ብንል ምን ይላችኋል? (አይዟችሁ አለመሳቅ መብታችሁ ነው!) አያችሁ --- ለጊዜው ዋጋው ያልተወደደ ቀልድ ብቻ ስለሆነ እሱም ድንገት ሳይንር ብንዝናናበት ነው የሚሻለን - በኋላ ቀልድ ድሮ ቀረ እያሉ መቆዘም እንዳይመጣ (እንደእነ ጥሬ ሥጋና ክትፎ ማለቴ እኮ ነው!) አሁን ቀልዱን እነሆ - በነፃ፡፡ አንድ ሴናተር ጠበቃው ቢሮ ውስጥ ተቀምጦ አዲስ ዜና ለመስማት በጉጉት ይጠብቃል። ጠበቃውም “ክቡር ሴናተር፤ መጀመርያ የትኛውን ዜና ልንገርዎ--- መጥፎውን ወይስ የከፋውን?” ሲል ይጠይቃቸዋል፡፡ ሴናተሩ ትንሽ ያስቡና “መጀመርያ መጥፎውን ልስማ---” ይላሉ፤ደግሞ ምን አመጣህብኝ በሚል ስሜት፡፡ ጠበቃም “ሚስትዎ ግማሽ ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ምስል እንዳገኘች ሰምቻለሁ” ይላቸዋል ሴናተሩ ተገርመው “ይሄን ነው መጥፎ ዜና ያልከው?እስቲ ደግሞ የከፋውን ያልከውን ንገረኝ ” ይሉታል በጥርጣሬ ዓይን እያዩት፡፡ ጠበቃውም “ምስሉ እኮ የእርስዎና የፀሃፊዎ ነው” አላቸውና እጢያቸውን ዱብ አደረገው፡፡

አያችሁልኝ ---- የቋንቋን ነገር! መግባቢያም መደናቆሪያም ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንዴማ ቋንቋውን የምናውቀው እየመሰለን ሁሉ የምንሸወድበት ጊዜ አለ፡፡ አሁን ለምሳሌ ከኢህአዴግና ከመንግስት ጋር በአንድ ቋንቋ የምናወራ ነው የሚመስላችሁ አይደል? እኔም እስከቅርብ ጊዜ ድረስ እንደዚያ ይመስለኝ ነበር፤ እውነቱ ግን ሌላ ነው፡፡ ኢህአዴግና መንግስት በአማርኛ ቋንቋ የሚያወሩ ቢመስሉም ፍቺው እኛ ከምንረዳው ፍፁም የተለየ ነው፡፡ ይሄኔ እኮ እያፌዝኩ ይመስላችሁ ይሆናል፡፡ ግን ከምሬ ነው፡፡ ኢህአዴግና መንግስት የራሳቸው ቋንቋ አላቸው ፡፡ የፓርቲ ኮድ የሚባል፡፡ ለዚያ እኮ ነው መግባባት ያቃተን፡፡ ያመናችሁኝ ስላልመሰለኝ አንዳንድ ማሳያዎች ማቅረብ ሳይኖርብኝ አይቀርም፡፡ ለናንተ ብቻ ሳይሆን ለራሱ ለኢህአዴግም ጭምር፡፡

እሱም ራሱ እኮ በኛ ቋንቋ የሚያወራ አድርጎ ነው የሚያስበው፡፡ በነገራችሁ ላይ ከዚህ የተገነዘብኩት አንድ ትልቅ ቁምነገር አለ፡፡ ምን መሰላችሁ? በአማርኛ ቋንቋ ስላወራን ብቻ እንግባባለን ማለት አይደለም፡፡ ሁለት ግለሰቦች በአንድ ቋንቋ እያወሩ ላይግባቡ ይችላሉ፡፡ እኛና ኢህአዴግ ምርጥ ምሳሌዎች ነን፡፡ (“እኛን ነው ማየት” ይሏል ይሄኔ ነው) ይኸውላችሁ ---- መንግስት በኢኮኖሚ ውስጥ እጁን ሲያስገባ እኔና እናንተ በስጋት ልንሞት እንችላለን - ያ የምንጠላው ሶሻሊዝም ተመልሶ ነፍስ ሊዘራ ነው ብለን፡፡ አንዳንዶቻችን ደግሞ መንግስት የዘበኝነት ሚና ብቻ ሊኖረው ይገባል በሚል ለመቃወም ሁሉ ይዳዳን ይሆናል (አለማወቅ ደጉ አሉ!) ለዚህ ሁሉ የዳረግን ግን ሌላ ሳይሆን የቋንቋ ችግር ነው፡፡ የኢህአዴግን ቋንቋ አለማወቃችን! አያችሁ ---- በኢህአዴግኛ መንግስት ኢኮኖሚ ውስጥ እጁን አስገባ ማለት ገበያውን አረጋጋ ማለት ነው (ቀላል ተሸወድን!) ትዝ ይላችኋል…ከፍተኛ የስኳር እጥረት የተከሰተ ጊዜ …”አሁንስ ክፉ ጊዜ መጣ!” ብለን ተስፋ ቆርጠን ነበር እኮ! ኢህአዴግ ነፍሴ ግን ከትከት ብሎ ሳቀብን (መሳቅ ሲያንሰው እኮ ነው!) የፓርቲ ቋንቋ ባለማወቃችን! ለካስ አገር ያተራመሰው የስኳር እጥረት ያን ያህል ጉድ የሚያሰኝ አልነበረም፡፡ ለምን መሰላችሁ? የስኳር እጥረት በኢህአዴግኛ የስኳር እጥረት አይደለም፡፡ ይልቁንም የኢትዮጵያ ገበሬ የስኳር ተጠቃሚ ሆኗል ማለት ነው፡፡

(ቋንቋ አለማወቅ እንዴት ያበሽቃል!) አሁን ተላመድነው እንጂ የኑሮ ውድነቱ መናር የጀመረ ጊዜ አበሻ “እግዚኦታ” ሊጀምር ምንም አልቀረውም ነበር፡፡ አውራው ፓርቲ ግን “ኧረ ለበጐ ነው!” እያለ ይማጠነን ጀመር፡፡ መቼም ኢህአዴግ ተዓምር አያልቅበትም አይደል (The Incredible የሚለውን ፊልም አይታችሁታል?) የኑሮ ውድነቱ እድገት ማለት ነው ብሎን ቁጭ አለ፡፡ ያኔ ተረጋጋን፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ባለሁለት ዲጂት ዕድገት በማሳየቱ የመጣ መሆኑን ስንሰማ ሃዘናችን ወደ ደስታ ተቀየረልን (ወይ ነዶ! የፓርቲ ቋንቋ አለማወቅ!) አያችሁ… ለእኛ የኑሮ ውድነት፣ በኢህአዴግ ቋንቋ ዕድገት ማለት ነው (ቀላል ተሸወድን!) ይኸውላችሁ…የእኛና የልማታዊ መንግስታችን ልዩነት ሌሎች እንደሚያስወሩብን ያን ያህል የተጋነነ አይደለም፡፡ ኢህአዴግ እንኳንስ ከእኛ ከመረጥነው ህዝቦቹ (ድምፆቹ ማለት እኮ ነን) ጋር ቀርቶ ለሥልጣን ከሚፎካከሩት ተቃዋሚዎችም ጋር የከፋ ጠላትነት የለውም፡፡

ችግሩ የቋንቋ ብቻ ነው፡፡ የፓርቲውን የኮድ ቋንቋ የሚያውቁት ቁንጮ የኢህአዴግ አመራሮች ብቻ ናቸው (ቁንጮ አመራሩ አድርባይ ሆኗል ነው የተባለው?) ለዚህ እኮ ነው ኢህአዴግና ህዝቡ ለሁለት አስርት ዓመታት መግባባት ያቃተው፡፡ ለምሳሌ ኢህአዴግ የበቆሎ ምርት በጥቂት ዓመታት ውስጥ ኤክስፖርት ማድረግ እንጀምራለን ሲል ልታፌዙበት ትችላላችሁ፡፡ እናንተማ ---- በቆሎ ከአገር ውስጥ ፍጆታ ተርፎ በምን ተዓምር ለውጭ አገር ገበያ ይቀርባል ብላችሁ ነው። እሱ ግን እንደዚያ ዓይነት ነገር አልወጣውም - እሱ ሊል የፈለገው በጥቂት ዓመታት ውስጥ “የበቆሎ ምርት እጥረት ጠብቁ ነው!” (የባቢሎን ቋንቋ ሆነባችሁ አይደል?) የኢትዮጵያ መብራት ሃይል ኮርፖሬሽን ከሁለት ዓመት በፊት ምን ነበር ያለን? የኤሌክትሪክ ሃይል ለጐረቤት አገራት ኤክስፖርት ማድረግ እንጀምራለን ሲለን ተገርመን አልነበር (በአማርኛ የሚያወራ መስሎን ነዋ!) ጊዜው ሲደርስ ግን የገጠመን ተደጋጋሚ የሃይል መቆራረጥ ሆነ፡፡ ኮርፖሬሽኑ ዋሽቶናል እያልኩ ግን እንዳይመስላችሁ፡፡ ችግሩ የእኛ ነው - ቋንቋ አለማወቃችን! ግን አንድ ነገር ልንክድ አንችልም፡፡

ኤልፓ ባይዋሸንም እኛ ግን በደንብ ተሸውደናል (በቋንቋ ዕውቀት ማነስ!) “ፓወር ኤክስፖርት አድርገን በፎርየን ከረንሲ እንንበሸበሻለን” ስንል በሻማና በፋኖስ ማዕድ መቅረብ ጀመርን! (ፈረንጅ ይሄ ነው “ዲዛስተር” የሚለው) ባለፈው ሚያዝያ ወር በተካሄደው የአዲስ አበባና የአካባቢ ምርጫም ተሸውደናል ልበል? (በደንብ ነዋ!) ምርጫ ቦርድ፤ “ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ይካሄዳል” ሲለን እውነት መስሎን በደስታ ጮቤ ረግጠን ነበር! ለካስ የቋንቋ ክፍተት የፈጠረው ችግር ነው፤ እንጂማ ቦርዱ “ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ይካሄዳል” ሲል ኢህአዴግ ያለተፎካካሪ ለምርጫው ይወዳደራል ማለቱ ነበር፡፡ መቼም በእኛ ቋንቋ አለማወቅ ቦርዱን መውቀስ “ፌር” አይደለም አይደል? በነገራችሁ ላይ በቅርቡ “የኢህአዴግና የህዝቡ ቋንቋ” የሚል ሳይንሳዊ መጽሐፍ ለማሳተም አስቤአለሁ (ኢህአዴግ ስፖንሰር ካደረገኝ) የአዲስ አበባ መስተዳድር በመዲናዋ የሚታየውን የትራንስፖርት ችግር ከደርግ በተኮረጀ የታክሲ ስምሪት (ቀጣና) እፈታለሁ ሲለን በጄ ብለን የተቀበልነው ቋንቋው ቀጥተኛ መስሎን እኮ ነው፡፡

ለካስ መስተዳድሩም በገዢው ፓርቲ የኮድ ቋንቋ ነው የሚግባባው፡፡ እናም “ታክሲ በቀጣና” የሚለው በኢህአዴግኛ “ታክሲ በወረፋ” አንደማለት ነው (የውጫሌ ውል ትዝ አላችሁ?) በዚህም የተነሳ ዛሬ ድረስ ጠዋትና ማታ ለታክሲ እንሰለፋለን (ቋንቋ አለማወቃችንን እያማረርን) በ2002 ምርጫ ኢህአዴግ ተቃዋሚዎችን በዝረራ ካሸነፈ በኋላ ምን ብሎ ነበር ያጽናናቸው? “ተቃዋሚዎች በፓርላማ መቀመጫ ባይኖራቸውም በአገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚሳተፉበት መድረክ ይመቻቻል” አላለም (ከዋሸሁ እታረማለሁ!) ያኔ ታዲያ ሁላችንም ደስ ብሎን ነበር - የጦቢያ ፖለቲካ ሊሻሻል ነው በሚል፡፡ ግን አሁንም ችግሩ የኛ ነበር፡፡ ኢህአዴግ በፓርቲው የኮድ ቋንቋ መናገሩን አልተገነዘብንም፡፡ ለካስ ተቃዋሚዎች በአገሪቱ ጉዳዮች ላይ ይሳተፋሉ ሲል ከእነ አካቴው ይገለላሉ ማለቱ ነበር (እውነትም የባቢሎን ቋንቋ!) በነገራችሁ ላይ ያለፉ ሁነቶችን እየነቀስኩ የኢህአዴግኛ ትርጉማቸውን ሰንግራችሁ ---- የፓርቲ ቋንቋ የምችል መስሏችሁ እንዳትሸወዱ! ሁሉንም ያወቅሁት ከህይወት ተመክሮ ነው፡፡ ነገርዬው ከሆነ በኋላ ማለት ነው፡፡ እንጂማ እኔን ለፓርቲ ቋንቋ ማን ያደርሰኛል (ካድሬ መሆንን ይጠይቃላ!) በቅርቡ አንዳንድ የመንግስት መ/ቤት አመራሮች በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ እያሉ የሚናገሩትን ሰምታችሁልኛል? ለምሳሌ ያቀዱትን በወቅቱ ማጠናቀቅ ያልቻሉበትን ምክንያት ሲጠየቁ ምን እንደሚሉ ታውቃላችሁ? “የአቅም ማነስ እንዳለብን አንክድም!” ይላሉ - አፋቸውን ሞልተው፡፡ ለምን እውነቱን ተናገሩ የሚል ነገር አልወጣኝም (እውነት ከሆነ አይደለ!) እኔን ያስገረመኝ ይሄን ሲናገሩ በጥፋተኝነት ስሜት አለመሆኑ ነው፡፡

በቃ የአቅም ማነስን ከአቅም በላይ እንደሆነ ችግር አድርገው ነው የሚያቀርቡት፡፡ ኢህአዴግ አንዳንድ ከቁጥጥሩ በላይ የሆኑ ችግሮች ሲገጥመው “ከደርግ የወረስነው ችግር ነው!” እንደሚለው፡፡ ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ…ካለፈው መንግስት በግድ የተላለፉ አንዳንድ ችግሮች እንደሚኖሩ መካድ አይቻልም፡፡ ለምሳሌ ድህነት፣ ደካማ የሥራና ኋላቀር የፖለቲካ ባህል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እንግዲህ ሳንወድ በግድ ከንጉሱም ሆነ ከደርጉ የወረስናቸውን ችግሮች እንደምንም ታግለን ከመፍታት በቀር አማራጭ የለንም፡፡ እኔን የሚገርመኝ ግን ካለፈው የደርግ ወታደራዊ መንግስት ወደንና ፈቅደን የወረስናቸው አንዳንድ አሰራሮችና ችግሮች ናቸው! ከወረስናቸው ችግሮች አንዱ ሶሻሊዝም ነው (ሶሻሊዝም ችግር እንጂ ምን ሊባል ይችላል!) ሌላው የታክሲ ቀጣና ነው - ወደንና ፈቅደን ከደርግ የወረስነው፡፡ ተሞክሮ የቀረውም የዋጋ ቁጥጥር ወደን የወረስነው ነበር፡፡ (ኢህአዴግ ሳያውቀው “ደርግ ናፋቂ” ሆነ እንዴ?) ወደንና ፈቅደን ችግር ከመውረስ ያውጣን እንጂ ሌላ ምን ይባላል!! በነገራችሁ ላይ ኢህአዴግ ዓለምአቀፍ ሚዲያዎችን እንዳይዘግቡ ከአገር ሲያስወጣ የፕሬስ ነፃነትን ያፈነ ከመሰላችሁ የቋንቋ ስህተት ፈፅማችኋል፡፡ በኢህአዴግኛ የአገር ገጽ ግንባታ ነው፡፡ ካፒታሊዝምን ሲያብጠለጥልና የደረሰባቸውን የኢኮኖሚ ድቀት ደጋግሞ ሲያነሳ ደግሞ “ፊቴን ወደ ቻይና አዙሬአለሁ” ማለቱ ነው፡፡ (በፓርቲው ቋንቋ ማለቴ እኮ ነው!) መልካም የዳግማይ ትንሳኤ በዓል እመኝላችኋለሁ!

አውሮፕላኖች በሚንደረደሩበት አውላላ ሜዳና ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግበት ኤርፖርት፣ የጥይት ድምፅ ሳይሰማ የተዘረፈው የ50 ሚሊዮን ዶላር አልማዝ፣ ከሶስት ወር የፖሊስ ክትትል በኋላ፣ ሰሞኑን ዱካው ተገኘ። ዝርፊያውን የፈፀሙ ስምንት ሰዎችን ከነተባባሪዎቻቸው ለመያዝና የተዘረፈውን አልማዝ ለማስመለስ በርካታ የአውሮፓ አገራትን ያዳረሰ ክትትል ሲያካሂዱ የከረሙ መርማሪዎች፣ በጣሊያን፣ በቤልጄምና በቱርክ ውጤት ቀንቷቸዋል። የካቲት 10 ቀን ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ነው በቤልጄም ዋና ከተማ ከሚገኘው የብራስልስ ኤርፖርት አልማዙ የተዘረፈው። ከኤርፖርቱ አጠገብ፣ ጅምር የህንፃ ግንባታ ውስጥ ተደብቀው ያመሹት ስምንቱ ዘራፊዎች፤ የኤርፖርቱን አጥር ሲተረትሩ ማንም እንዳያያቸው ተጠንቅቀዋል። ወደ ውስጥ ከገቡ በኋላ ግን፣ በድብቅ ለመሽሎክሎክ አልሞከሩም። በተተረተረው አጥር ሁለት ጥቋቁር መኪኖችን እያሽከረከሩ ወደ አውሮፕላን መንደርደሪያው አመሩ።

ስምንቱ ዘራፊዎች እንደ ፖሊስ ለብሰው መሳሪያ ታጥቀዋል። በእርግጥ መሳሪያቸው የቤልጄም ፖሊሶች የሚጠቀሙበት አይነት ሳይሆን ክላሺንኮቭ ነው። ግን ከርቀት ይህንን ለይቶ የሚያስተውል አይኖርም። የፖሊስ ታርጋ የተለጠፈባቸው ሁለቱ ጥቋቁር መኪኖች፣ ኮፈናቸው ላይ ሰማያዊ የፖሊስ መብራቶች ተተልክሎላቸዋል። ማንም አላስቆማቸውም። በቀጥታ የአውሮፕላን መንደርደሪያዎችን እያቆራረጡ፣ ወደ ስዊዘርላንድ ለመብረር የተዘጋጀች መካከለኛ አውሮፕላን ጋ ደረሱ። ሌላ መኪና ለትንሽ ቀድሟቸዋል። ከእቅዳቸው ዝንፍ ያለ ነገር የለም። ከነሱ ቀድሞ የደረሰው መኪና፣ እንደ ካዝና በጠነከሩ ብረቶች የተሰራ የውድ እቃዎች ማመላለሻ ነው - ውድ የአልማዝ ጠጠሮችን ወደ አውሮፕላኑ የሚያደርስ። የመኪናው በር ተከፍቶ፣ እፍኝ እፍኝ የማይሞሉ 130 የአልማዝ ከረጢቶች ወደ አውሮፕላኑ ለማስገባት… ከዚያም አውሮፕላኑ ተነስቶ ለመብረር፣ ከ15 ደቂቃ በላይ መዘግየት እንደሌለበት ትዕዛዝ ተሰጥቷቸዋል። ዘራፊዎቹ ትክክለኛ መረጃ ባይኖራቸው ኖሮ፣ በትክክለኛው ሰዓት ባልደረሱ ነበር።

የአልማዝ ከረጢቶቹ ወደ አውሮፕላኑ ከገቡ በኋላ ለበረራ ሊነሳ ሲል ሁለት መኪኖች ከተፍ አሉ። የፖሊስ የደንብ ልብስ አድርገው፣ ፊታቸውን በጭንብል ሸፍነው፣ መሳሪያቸውን ወድረው ወደ አውሮፕላኑ የተንደረደሩት ዘራፊዎች፣ ፓይለቱንና የጥበቃ ሰራተኞችን በማስፈራራት የወርቅ ከረጢቶቹን ለመውሰድ ጊዜ አልፈጀባቸውም። በ20 ደቂቃ ውስጥ 50 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ የአልማዝ እንቁዎችን ይዘው እንደአመጣጣቸው ተፈተለኩ - ግርግር ሳይፈጠር፣ የጥይት ድምፅ ብቻ ሳይሆን የሃይለ ቃል ድምፅ ሳይሰማ ዘረፋው ከመጠናቀቁ የተነሳ፤ ተሳፋሪዎቹ ምን እንደተፈጠረ አላወቁም። በረራው እንደተሰረዘና ዘረፋ እንደተፈፀመ ሲነገራቸው ማመን አልቻሉም ነበር። ስምንቱን ዘራፊዎች ከነተባባሪዎቻቸው ለመያዝ በበርካታ የአውሮፓ አገራት ለሶስት ወራት ሲካሄድ የቆየው የፖሊስ አደን፣ በዚህ ሳምንት በከፊል ውጤታማ ሆኗል።

ከዘራፊዎቹ መካከል አንዱ በጣሊያን ከ8 ተጠርጣሪ ተባባሪዎች ጋር የተያዘ ሲሆን፤ በስዊዘርላንድ ሌሎች ተባባሪዎች በቁጥጥር ስር ሲውሉ የተወሰነው ያህል አልማዝም ተገኝቷል። በቤልጄም ደግሞ ከሃያ በላይ ሰዎች ታስረዋል። በኤርፖርቱ የተፈፀመው ዝርፍያ፣ በታሪክ ከተመዘገቡ ትልልቅ የአልማዝ ዝርፊያዎች መካከል በሁለተኛ ደረጃነት የሚጠቀስ ቢሆንም፤ አልማዝን ማጓጓዝ ግን ለቤልጄም ኤርፖርቶች የእለት ተእለት ስራ ነው። በአለማችን ለገበያ ከሚቀርቡ የአልማዝ ጌጣጌጦች መካከል ግማሽ ያህሉ ቤልጄምን ሳይረግጥ አያልፍም - የአልማዝ ማዕድን ተሞርዶና ተጣርቶ አምሮበት የሚወጣው ቤልጄም ውስጥ በሚገኙ ኩባንያዎችና ባለሙያዎች ነው። በየእለቱ፣ ቤልጄም በአማካይ የ200 ሚሊዮን ዶላር አልማዝ ታስተናግዳለች።

Published in ዜና

ከካህሊል ጂብራን አጫጭር ተረቶች አንዱ እንደሚከተለው ይላል፡- አራት ባሪያዎች አንዲትን ያረጀች ንግሥት በተኛችበት ያራግቡላታል፡፡ ንግሥቲቱ የተኛችው ዙፋኗ ላይ ነው፡፡ ታንኮራፋለች፡፡ እጭኗ ላይ አንዲት ድመት ወደ ባሪያዎቹ በዳተኛ አስተያየት እያየች ባሪያዎቹ ለሚነጋገሩት ምላሽ ትሰጣለች - በድመትኛ! አንደኛው ባሪያ “ይህቺ አሮጊት እንቅልፍ ሲወስዳት መልኳ እንዴት ያስጠላል፡፡ ለምቦጯ እንዴት ተንጠልጥሏል፡፡ ደሞ ኩርፊቷ ዲያብሎስ ሠርንቆ የያዛት እኮ ነው የሚመስለው” አለ ይሄኔ እመት ድመት ሚያው ሚያው አለች፤ በድመትኛ፡፡ ትርጉሙም - “ከአንተ ካልተኛኸውና ነቅተህ ባሪያ ሆነህ ከምታስጠላው የበለጠ አስታጠላም አለችው፡፡ ሁለተኛ ባሪያ “እንቅልፍ፤ የተጨማደደ ቆዳዋን የሚያቃናላት መሰላት እንዴ? የባሰኮ ነው የሚያጨማድዳት! የሆነ የተንኮል ነገር ነው መቼም እያለመች ያለችው” ይሄኔ እመት ድመት ሚያው ሚያው አለች በድመትኛ፡፡

ትርጉሙም - “እስቲ አንተም ተኛና ስለነፃነትህ አልም” ሶስተኛው ባሪያ ደሞ ተናገረ - “ምናልባት እስከዛሬ ያረደቻቸውን ሰዎች የቀብር ስርዓት እያየች ይሆናል” እመት ድመት በድመትኛ ቋንቋ ሚያው ሚያው አለች፡፡ “አሄሄ! እሷማ የምታየው የአያት ቅድመ አያትህንና የልጅ ልጆችህን ቀብር ነው!” አራተኛው ባሪያ እንዲህ አለ - “ስለ እሷ መናገራችን ጥሩ ነው፡፡ እዚህ ተገትሮ ለእሷ ማራገብ ግን በጣም ይደክማል” እመት ድመት በሚያው ሚያውኛ መለሰች፡፡ “ገና ዕድሜ-ልክ ታራግባለህ፤” ደሞም በመሬት የሆነው በመንግሥተ ሰማይም ይደገማል” ልክ ይሄን እያወሩ ሳሉ አሮጊቷ ንግሥት የሰማች ይመስል፤ በእንቅልፍ ልቧ እራሷን በአዎንታ ነቀነቀች፡፡ ዘውዷም ከጭንቅላቷ ተንሸራቶ መሬት ላይ ወደቀ፡፡ ከባሪያዎቹ አንዱም፤ “ኧረ! ይሄኮ መጥፎ ምልኪ ነው” አለና ሟርቱን አሰበ፡፡ እሜት ድመትም በሚያው ሚያውኛ “ያንዱ መጥፎ ምልኪ ለሌላው በጐ ምልኪ ነው” አለች፡፡

ሁለተኛው ባሪያም፤ “አሁን ብትነቃና ዘውዱዋ መውደቁን ብታይስ ጐበዝ! ሁላችንን ታርደናለች” እመት ድመት በሚያው-ሚያውኛ - “ከተወለዳችሁ ከመጀመሪያ ቀን ጀምሮ ስታርዳችሁ ነው የኖረችው፡፡ ችግሩ፤ አይታወቃችሁም” ሦስተኛው ባሪያም እንዲህ አለ “አዎን ታርደናለች፡፡ ስሙንም ለአማልክት የሚከፈል መዋስዕትነት ትለዋለች” እመት ድመትም በሚያው ሚያውኛ “ደካሞች ብቻ ናቸው የአማልክት መስዋዕት የሚሆኑት” አለች፡፡ አራተኛው ባሪያ ሌሎቹን አፋቸውን አዘግቶ በእንክብካቤ ዘውዱን አንስቶ፤ አሮጊቷ ንግሥት እንዳትነቃ አድርጎ መልሶ ጫነላት፡፡ እመት ድመትም በድመትኛ ተናገረች፡- “እንዴ የወደቀን ዘውድ መልሶ የሚያነሳ ባሪያ ብቻ ነው” አለች፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ንግሥቲቱ ነቃች፡፡ አካባቢዋን አየች፡፡ አዛጋችና፤ “በህልሜ አንድ ዋርካ ሥር አራት አንበጦችን አንዲት ጊንጥ ስታባርራቸው አየሁ፡፡ ጥሩ ነገር አይመስለኝ ህልሜ” አለች፡፡ ይሄን ብለ መልሳ አንቀላፋች፡፡ ማንኮራፋቷንም ቀጠለች፡፡ አራቱ ባሪያዎችም ማራገባቸውን ቀጠሉ፡፡ ድመቷም በሚያው-ሚያውኛ ቋንቋ፤ “ቀጥሉ፡፡ ማራገባችሁን ቀጥሉ፡፡ምድረ-ደደብ ሁሉ ቀጥሉ!! የምታራግቡት እናንተኑ የሚበላችሁን እሳት ነው፡፡ ቀጥሉ!!”

                                                            * * *

ካልተኛኽ ግን ባሪያ ሆነህ የቀረኸው፣ የተኛ ይሻላል፤ ከመባል ይጠብቀን፡፡ አንድ ግፍ አያት-ቅድመ አያታችንን ያጠፋው ሳያንስ፤ ለልጅ ልጆቻችን ከተረፈ ከእርግማን ሁሉ የከፋ እርግማን ነው! የማራገብ አደጋ ለሀገርና ለህዝብ የማይበጅ ፅኑ ጠላት ነው፡፡ በቀላሉ ተዋግተን ልናጠፋው ከቶ አንችልም! በተለይም ደግሞ የምናራግበው እኛኑ መልሶ የሚፈጀንን ከሆነ አሳሳቢ ነገር ይሆናል፡፡ የተውነውን፣ የጣልነውን፣ አንዴ የተላቀቅነውን አስተሳሰብ መልሰን ለማንሳት ከመሞከር ያድነን፡፡ የአሸነፍነውንና የተገላገልነውን አስተሳሰብ መልሰን ለማስተናገድ ዝግጁ አለመሆን ብልህነት ነው፡፡ ከዘመነ-መሣፍንት እስከ ነጋሲው አገዛዝ ድረስ፣ አልፎም ከወታደራዊው ሶሻሊዝ ወዲህም እስከ ብሔር-ብሔረሰባዊ ዲሞክራሲ ድረስ ረዥም መንገድ ሄደን፤ ሕግና ሥርዓት ልናስከብር፤ የሻይ ቤት የኬክ ቤት አገር ሳይሆን ትልቅ ኢንዱስትሪ ልንገነባ፤ በምንም ዓይነት ሰው ለሰው የማይበዘበዝባት፣ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር የሚሰፍንባት፣ እኩልነት ያረበበባት፣ ዘረፋና ውንብድና የማይታይባት፣ ሉዐላዊነቷ የተከበረ ቆንጅዬ አገር ልንመሰርት፤ ቃል ከገባን ውለን አደርን፡፡

በረዥሙ መንገድ ላይ አንዳንዶቹ ተሳክተው “እሰይ አበጀህ የእኛ ሎጋ” ሲያሰኙን፣ ሌሎቹ ከሽፈው ምነው ባልነካካናቸው ኖሮ አሰኝተው አንገታችንን ሲያስቀረቅሩን፤ የውሾን ነገር ያነሳ ውሾ ይሁን ሲያስብሉን እዚህ ደርሰናል፡፡ አሁንም ቢሆን “አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ” ነውና፤ ዐይናችን እያየ የተፋጠጡንን የሙስናና የመልካም አስተዳደር አደጋዎች እንዲሁም የሚሥጥራዊነት አባዜ (ከግልፅነት አንፃራዊ በሆነ አቋም - as opposed to እንዲሉ) ካልተዋጋንና ወደ ግልፅ ውንብድና ሊሸጋገር አንድ አሙስ የቀረውን የሥርዓት-አልባነት፣ የሌብነትና የጭለማ-ሽምቅ ዘረፋ (ለአፍሪካ ህብረት 50ኛ ዓመት በዓል ሰሞን ብቻ ሳይሆን ለዘለቄታውም ልንፋለመው ብንፈጠም መልካም ነው፡፡

ገንዘብ እንዴት ልሰብስብ እያልን ገንዘብ ሲዘረፍ አላየሁም ማለት መቼም አያዋጣንም፡፡ እስከ ናይጄሪያና ኬንያ ዘረፋ ድረስ የከፋ ደረጃ አልደረስንም ብለን መፅናናት አንችልም፡፡ ጥፋት እያባረረን ነው፡፡ ጥፋቱ እስካለ ድረስ ሸሸን ማለት ከንቱ ነው፡፡ ለዚህ ነው “አሳዳጅ ካልተወ የሸሸ መች አመለጠ” የሚባለው፡፡ “…ትቻቸዋለሁ ይተውኝ አልነካቸውም አይንኩኝ ብለህ ተገልለህ ርቀህ ዕውነት ይተውኛል ብለህ እንዴት ተስፋ ታደርጋለህ? የተወጋ በቅቶት ቢተኛ፣ የወጋ መች እንቅልፍ አለው የጅምሩን ካልጨረሰው…” እንዳለውም ነው ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን፡፡

Published in ርዕሰ አንቀፅ

ራስህን አስተዋውቀን -- ጥጋቡ ቸርነት ወይም መሃመድ ---- እባላለሁ፡፡ ጥጋቡ የቤት ስምህ ነው? ዋ! ቤተሰቦቼ እኮ ሙስሊሞች ናቸው፡፡ አያቴ መሃመድ ነበር የሚለኝ፡፡ ያው እኔ ተጠምቄ ነው፡፡ አንዳንዶች አሽቃባጭ፣ ፋረኛው ራፐር፣ ይሉኛል፡፡ እኔ ግን ራሴን የምጠራው ‹‹አዳማቂው›› በሚል ነው፡፡ በፆም ወቅት ስንት ስራዎች ሰራህ?

አሁን ድምፃውያን ሙሉ ስራ ላይ ብዙም ትኩረት እየሰጡ አይደለም፡፡ ሞያተኛውም ሰርቶ ጥቅም ባለማግኘቱ፣ የኮፒራይቱም ጥሰት ተጠናክሮ በመቀጠሉ ወደ ነጠላ ዜማና ክሊፖች ነው አርቲስቱ እያዘነበለ ያለው፡፡ ወደ አስር ነጠላ ዜማዎች ላይ ተሳትፌአለሁ። የታዋቂዎችና የጀማሪ ባህላዊ ዘፈኖች ላይ ሰርቻለሁ፡፡ ለፋሲካ ባህል የሚወጡ ነጠላ ስራዎች አሉ፡፡ እንዴት ነው ሥራውን የጀመርከው፣ አርአያ የሆነህ ባለሙያ አለ? እገሌ የምለው የለኝም፡፡ ፈር ቀዳጅ አዳማቂ---- ፈር ቀዳጅ አሽቃባጪ በይው!! ..በገጠር ነው እድገቴ፡፡ በሀገራች ሁሉ አቀንቃኝ፣ ሁሉ ጨዋታ አዋቂ፣ ነገር አዋቂ፣..እንደመሆኑ በሰርግም ሆነ በጥምቀት አንዱ ግጥም ሲሰጥ፤ አንዱ ሲቀበል…ሌላው ሲፎክር፣ ሲሸልል…የውስጡን ስሜት በተረትና በምሳሌ ይገልፃል የባላገር ህይወት ይሄው ነው፡፡ በጋራ ሸንተረሩና በየመንገዱ ላይ .. ማንጎራጎር የተለመደ ነው፡፡ ቆይ ቆይ እንደውም አስተውለሽ እንደሁ --- እዚህ አገር እኮ ይመጡልሻል---- ከገጠር አካባቢ ---‹‹ሸበላው›› የሚባሉትን እስኪ ጠጋ ብለሽ ስሚያቸው---- ትርጉም የሌለው ዝም ብሎ ብቻ እንደሙዚቃ መሳሪያ ሲሉት…የድምፃቸው ማማር፡፡

/በድምፁ እያንቆረቆረ/ ገጠር የት ነው የተወለድከው፣ ያደከው? የተወለድኩት ጎንደር ነው፡፡ ያደግሁት ግን ባህርዳር። ጎንደር እፍራዝ ደንቢያ ፍርቃ ይባላል፡፡ ….. እናልሽ-----ገና ህፃን ሳለሁ ------ ወላጆቼን በሽታ ጨረሳቸው፡፡ በወቅቱ በሽታ ገብቶ ነበር፡፡ በሰዓቱ ብዙ ከብትና ሰው አለቀ፡፡ ስምንት የወንድ አያቴ ልጆች ሞቱ፣ እናቴም ሞተች፣ የእናቴ እናት ሞተች…የተወሰኑ ሰዎች ስንቀር “አያቴ እነዚህን ላትርፍ፣ ዘሬን ላጣ ነው፣ እኔም ብሞት አጉል ነው” ብሎ የተወሰኑትን ቤተዘመዱን ይዞ ባህርዳር ገባነ፡፡ ባህርዳር ነው ያደኩት፡፡ አያቴ ነው ያሳደገኝ፡፡ አንተ ያን ጊዜ ስንት ዓመትህ ነበር? ወደ ሰባት ብሆን ነው፡፡ ብዙም ትዝ አይለኝ፡፡ የተወለድክበት ገጠር፤ ትዝታው የለማ? የተረፈው ዘመድ ተርፎ አሁን አሁን ሰርግ ይጠሩኛል እሄዳሁ፡፡ አንዳንድ የሩቅ ዘመዶችም ቢሆኑ አይጠፉም፡፡ ዋ!! መቼም አልተለየሁም ከገጠር፡፡ ሰርግ ላይ ተጠርተህ ስትሄድ ታቀነቅን ነበር ታዲያ? ዋ..ማ ብሎኝ---አስነካው፡፡ ‹‹እረ ፈሪ ብልጡ፣ እረ ጃርቲ ብልጡ ሲሮጥ የሚያይበት፣ አይን አለው በቂጡ ነፋስ ዶቄት ሰርቆ አይበላው አንጉቶ(2) ወደልሽ ሰደበኝ የአንቺን ነገር ሰምቶ…›› እያልን ለማማለል ..በሰርግ በዚያው የራስንም ለማግኘት..ጥቅሻው ይደራል፤ በግጥም መነቋቆሩ ይኖራል…በዚህ ጊዜ ‹‹አይ ድምፅ፣ አይ እስክስታው፣ አይ አንገቱ..›› ይባላል፡፡

የገጠር ሰርግ በከበሮ፣ በጡሩንባ፣ አጀቡ ሌላ ነው.---- አሁን “በሙሉ ባንድ ሙዚቃ ሰራን” ከሚባለው ኪነት እንኳን ድምቀቱ ሌላ እኮ ነው!! ተቀባዩ ብትይ፤ አድማቂው ሌላ እኮ ነው፡፡ ከዛ ፊት ግን ባህርዳር በልጅነቴ ገብቼ በእርሻው በከብት ጥበቃ ስራ ተሰማርቼ ባላየውም፣ የእኔ መኖሪያ ከከተማ ወጣ ይል ስለነበር አባይን ተሻግረን ‹‹ማክሰኝት..ዘንዘልማ›› የሚባል ቦታ እንሄድ ነበር፣ ከእኩዮቼ ጋር እንውል የነበረው ከአራዊትና ከእንስሳቱ ጋር በድር ነው። ልብሳችንን እናወልቅና ጭንቅላታችን ላይ ጠመጥመን..አባይን በዋና አቋርጠን ዶቅማ፣ ሾላ፣ እንኮይ፣ እሸ…” የተባሉ ፍራፍሬዎችን …እንለቅማለን፡፡ ከጠዋት እስከ ማታ ስንጫወት እናመሻለን፡፡ ጠላቂ፣ ዋናተኛ ነህ? ስሚ አባይን እኮ በዋና አቋረጥሽ ማለት ሌላ ሳይንስ ነው፡፡ ውሃው ሲወርድ እኮ እንዴት እንደሚማታ ..ብዙ ሰዎችን ያሳስታል፡፡ አልፎ ስታይው ድንጋይ ነው የሚመስልሽ፡፡ እና ሰዎች የአባይን ባህሪ ስለማያውቁት ቅርብ እየመስላቸው ስንቱን ውሃ በላው መሰለሽ። አንድ ቦታ የሚወርድ ይመስልሽና በደለል የተሸፈነ ወይንም በድንጋይ ይሆናል፡፡ አንድ ጊዜ ከጭንቅላቴ የማይወጣ እስከዛሬም ሳስበው ድርጊቱ ዝግንን የሚለኝ ነገር ገጥሞኛል።

በደርግ እና በኢህአዴግ ጦርነት ጊዜ የደርግ ሰራዊት በአባይ ተበልቷል፡፡ ጦርነቱ ሲገፋ ከኢህአዴግ ሰራዊት ለማምለጥ ብለው ሊሻገሩ እጅ ለእጅ ተያይዘው ሲሄዱ ጠርጎ ሲወስዳቸው ትዝ ይለኛል፡፡ ዋናማ ለገጠር ልጅ ምኑ ነው፡፡ ያውም በአባይ ወንዝ ዋናን የለመደ፡፡ እኛማ ዝም ብለን አይደል ጠልቀን እምንሄድበት፡፡ አባይን ተሻግረን ቤዛዊት የሚባል የአፄ ሃይለስላሌ ቤተመንግስት አካባቢ በዋና እንወጣና በዱር በገደሉ ከዝንጀሮዎችና ከአራዊቱ ጋር እናመሻለን፡፡ ከዝንጀሮ ጋር ግብ ግብ ገጥመን ነው ያልኩሽን ፍራፍሬ የምንመገብ፡፡ እንደ ዝንጀሮ ተንኮለኛ የለም፣ ዝንጀሮን “አንዳንድ ተንኮለኛን ሰው ይመስላል” ሲሉ እሰማ ነበር፡፡ ዝንጀሮው ፍራፍሬውን ስንለቅም ተራራ ላይ ሆኖ ድንጋይ ይወረውርብናል፡፡ ከተራራ ላይ ሆኖ የድንጋይ ናዳ ይለቅብናል፡፡ አንድ ጓደኛዬ ዝንጀሮ ፈንክቶታል፡፡ እኛ ግን እንደ ጨዋታም ስለምናየው ከዝንጀሮው ዱላ ይልቅ እናቀነቅናለን…ድምፃችን ከገደል ገደል እየተላተመ፤ ከተራራ ተራራ እየተጋጨ የሚያሰማን የገደል ማሚቱ አይነት ነገር የራሳችንን ድምፅ እንድናውቀው፣ እንድንወደው ይረዳናል፡፡ ደጋገምን እንጮሃለን፣ እንዘፍናለን…ተፈጥሮ በራስዋ ከእኛ ጋር ስታውካካ ታመሻለች፡፡ ዋ!! ያልሽ እንደሆነ እኮ ደግሞ አንዱ ግጥም ሲሰጥ፣ አንዱ ሲቀበል ሲፎከር ሲሸለል ሳናውቀው ቀኑ መሽቶ ይነጋል፡፡ አመሻሻችንን ደግሞ በዋና ተመልሰን ወደ ሰፈራችን እገባለን፡፡

ዛሬ ፅፌ እንኳን ሙዚቃ አልይዝም፣ ያን ጊዜ ግን ምኑን ልንገርሽ፡፡ ቴፕ እንኳን በቤታችን ስለሌለ አዲስ ካሴት የምንሰማው ሙዚቃ ቤት ደጅ ላይ ቆመን ነበር። አንድ ሙሉ ካሴት ጀምሮ እስኪያልቅ…አንዳንድ ጊዜም የሙዚቃ ቤት በር ላይ እንደቆምን፣ አንድ ካሴት ብቻ እየተገለባበጠ እየሰማን ይመሻል፡፡ ሙዚቃ ቤቶችም እንደማሻሻጫ ሰው ሰምቶና አይቶ እንዲገዛቸው ስለሚፈልጉ ነው መሰለኝ…. እንደ ጉንዳን ሱቁን ከበን በምሳጤ ስናዳምጥ፤ አንዳች አይናገሩንም…ጭራሽ ካሴቱን እየገለባበጡ ያስደምጡናል፡፡ .. ማድመጥ ብቻ ነው ወይንስ ያደመጥከውን የባህል ምሽት ቤቶች እየዞርክ ታንጎራጉራለህ? ያን ጊዜ የምሽት ክበብ ብዙም አይታወቅም፡፡ እኔንም እዛ የሚያደርሰኝም የለ፡፡ ልጅ ነኝ!! በየጠላ ቤቱ እየተዘዋዟርኩ ሳቀነቅን፤ ስሸለም ነው የምውለው፡፡ ሰው ልብስ አጠባ ወንዝ ይወርዳል፤ ሲወርድ እኔም ወንዝ ወርጄ ስዘፍን ይሸልሙኛል፡፡ የትምህርትህስ ነገር ----- መማር እስከ ስምንተኛ ክፍል ተምሬያለሁ፡፡ ግን ድህነቱም ስለነበረ ቀን ቀን ሊስትሮ እየሰራሁ ምሽት ወደ ጠላ ቤት እየሄድኩ በግጥምና በማቀንቀን ጠጪውን ሳዝናና፣ በየሙዚቃ ቤቱ የሰማሁትን የነጥላሁን ገሠሠን ዘፈን ሳንጎራጉር --- አልኩሽ ሽልማቱ ይዥጎደጉድልኝ ጀመር፡፡

ጠላም ያልሽ እንደሆን ያን ጊዜ ርካሽ ነው፣ አንዱ ማንቆርቆሪያ 25 ሳንቲም ነበር፡፡ ገንዘቡ እየተጠራቀመ ሲመጣ --- መቶና ከዚያም በላይ በቀን ሳገኝ ..ደርሼ እያማረብኝ መጣ፡፡ አንድ ቀን ግን እዚያው የምሽት ክበብ/የምሰራበት ጠላ ቤት/ ውስጥ አንድ እክል ገጠመኝ፡፡ ምን ገጠመህ? ያን ግዜ ደረስን ደረስን የሚሉ ቡጢኛዎች ከምኖርበት ከከተማ ወጣ ብሎ ከሚገኘው ሰፈሬ አካባቢ የሚገኙ ልጆች ያዙኝና ከዛሬ ጀምሮ እኛ በምንሄድበት ትሄዳለህ፤ የምንልህን ትፈፅማለህ፡፡ ከአሁን በኋላ በየጠላ ቤቱ እየሄድክ ብትዘፍን ውርድ ከራሳችን አሉኝ፡፡ ‹‹እንዴት?›› ስላቸው ‹‹በቃ ጠላ ቤትም ቢሆን ከእኛ ጋር እንጂ ዝም ብሎ መንከውከው አይቻልም›› አሉኝ፡፡ ክብደት ያነሳሉ፣ ደረታቸውን ውጥርጥር አድርገው ሲጓዙ በጣም ያስፈራሉ፡፡ ቢደበድቡኝስ ብዬ ቀን ቀን ሊስትሮዬን እየሰራሁ፤ ማታ ማታ ከእነሱ ጋር በየጠላ ቤቱ እዞር ነበር፡፡ እነሱ ካልከፈቱኝና ከልዘጉኝ በስተቀር እኔ አንዳች መተንፈስ አልችልም ነበር፡፡ ማለት? ጠላ እየጠጣን የጠላ ቤት ታዳሚው ከዚህ ፊት እዘፍን እንደነበረ የሚያውቀው ሁሉ እኔን ሲያይ፤ ግብጦውን እና ቦቀልቱን ከጠላ ጋር እያሻመደ.. እሱ ምን አለበት… ‹‹አንተ ምነ ዛሬ ልሳንህ ተዘጋ፡፡ በል እንጂ አቀንቅን›› ይሉኛል፡፡ ልሳኔን በቡጢኞች ሊያዘጋ ስለሚችል ቃል አልተነፍስም፡፡ ከቡጢኞች መካከል አንዱ ተንስቶ ‹‹እራ….እኛ ሳንከፍተው ሳንዘጋው አያቀነቅንም›› ይላል፡፡ በኋላ እንደ ቡጢኞች መልካም ፈቃድ ትከሻዬን በአውራጣቱ ጫን ብሎ ‹‹ቀጭ›› ይለኛል፡፡ በእርሱ ቤት ቴፕ እንደመክፈትና እንደ መዝጋት ነው፡፡

ያን ጊዜ መዝፈን እጀምራለሁ፡፡ እንደገና ‹‹ቀጭ›› ሲለኝ ስዘፍን የነበርኩት አቋርጣለሁ፡፡ ጠላ ቤት ይዘውኝ የሚሄዱት 25 ሳንቲም፣ 50 ሳንቲም ሲያገኙ ነው፡፡ ያም ሳንቲም ሆኖ የሚጠፋበት ጊዜ ነበርና አንዳንድ ጊዜ ወንዝ ይዘውኝ ይወርዳሉ፡፡ እነሱ እየታጠቡ ..እነሱን እኔ አዝናናለሁ፡፡…ወንዝ ይዘውኝ ወርደውማ..ቴፕን እስከ መጨረሻው እንደመክፈት ቁጠሪው‹‹…ድምፅህን ጎላ አርገህ ዝፈን…አትሰማም…ቀይር…አቅጥን …አወፍር…›› ሲሉኝ -- ስዘፍን አንዱን ስል አንዱን ስጥል እውላለሁ፡፡ ስራም አልሰራሁ፣ እነሱ ወደ ቤታችው ሲሄዱ እኔ የምበላውም አይኖረኝ፣ አንጀቴን አጥፌ እውላለሁ፡፡ በጣም መቸገር ጀመርኩ፡፡ ‹‹የፈለገው ይምጣ›› ብዬ ጠፍቻቸው ሊስትሮዬን መስራት ጀመርኩ፤ የመንግስት ሰራተኞች ከቤታቸው መስሪያ ቤታቸው ምሳቸውን አደርሳለሁ --- በዚህ በዚህ ገንዘብ ማግኘት ጀመርኩ፡፡ አንዱ ቀን ከእነሱ ጋር ጠላ ቤት ሂጄ ‹‹ለምን ገንዘብ አዋጥተን ልብስ አንገዛለትም›› ብለው ጠላ ቤት ውስጥ የብር መሰብሰቢያ ሰሃን አስቀምጠው፣ የጠላ ቤቱ ሰው ሁሉ አዋጥቶ በወቅቱ ፋሽን የነበረ እንዴት ያለ ማራዶና ቱታ ከአዲዳስ ጫማ ጋር ገዙልኝ፡፡

አቤት ከእኔ በላይ ሰውም ያለ አልመስል አለኝ፡፡ እዚያው ጠላ ቤት ነው እድሌ የወጣች ..አንዱ ቀን እዚያው ጠላ ቤት ስዘፍን የ‹‹ባህርዳር ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ/ኮተኒ›› ይባላል፤ የዛ መስሪያ ቤት ሰራተኛ የሆኑ ሰዎች አለቆች አገኙኝ ፣ በወቅቱ ፋብሪካው ኪነት ነበረው፡፡ ሙዚቀኛ ይፈልጉ ነበር፡፡ ሲያዩኝ ‹‹አንተ እንደዚህ በየጠላ ቤቱ እየዘፈንክ ዝናህን ሰምተን ነበር..እንዴት ያለኸው ልጅ›› አሉና ይዘውኝ ሄዱ..በፋብሪካው ለነበረው የኪነት ቡድን በወጣ ማስታወቂያ ከተወዳደሩ ሁለት መቶ ሰዎች መካከል አንደኛ በመውጣት ተቀጠርኩ፡፡ በስንት ብር ደሞወዝ? ደሞዝ? ከቴም ደሞዝ!! እረ የለውም፡፡ የኪስ ገንዘብ ነው፤ 50 ብር፡፡ ጠላ ቤት በቀን የምታገኘው አይበልጥም---- በ50 ብር ከምትቀጠር? እሱማ ነው ግን--- የመንግስት ስራ ነው፡፡ ከቀን ቀን ይሻሻል ብዬ በማሰብ እንጂ ምን አከላት አለው ብለሽ ነው 50 ብር፡፡ በ50 ብር ስንት ዓመት ሰራህ? አራት ዓመት ሰራሁ፡፡

ግን ከሸክም እስከ ሊስትሮ ብቻ ህይወት እንድትቀጥል የሚያስችላትን የትኛውምን ገንዘብ የሚያስገኝ ስራ እሰራ ነበር፡፡ ከዚያ እዚያው ባህርዳር ጊሽ ዓባይ ኪነት ማስታወቂያ አወጣ- ተወዳድሬ አለፍኩ፡፡ በድምፃዊነት ነው? በድምፃዊነት ነበር ያለፍኩት ግን ‹‹ሁለገብ መሆን ያስፈልግሃል›› ተብዬ ወደ ውዝዋዜውም ገባሁ፡፡ በመቶ ሃያ ሰባት ብር ነበር የተቀጠርኩት፡፡ እነ ሰማኸኝ በለውን፣ ይሁኔ በላይን፣ ስፈልግ አያሌውን፣ እነ ወይኒቷን ያፈራ ኪነት ነው፡፡ ጊሽ ዓባይ ኪነት ወደ አራት ዓመት ሰራሁ --- ግን እሱም ወዲያው ኢህአዴግ ገባና ኪነቱም ተበተነ፡፡ በጊሽ ዓባይ ኪነት በነበረህ ቆይታ ጦሩን ለመቀስቀስም ወደ ጦር ግንባር ከቡድኑ ጋር የመውጣት እድል አግኝተህ ታውቅለህ? አንዱ ጊዜ ወደ አስመራ ጦሩን ለመቀስቀስ ሲኬድ የመሄድ እድል ገጥሞኝ ነበር፣ ነገር ግን ተመካክረው ቀነሱኝ፡፡

‹‹ልጅ ነው--- በረሃ ውሃ ጥም አይችልም›› ብለው፡፡ ከዚያስ የአንተ እጣ ፋንታ ምን ሆነ? ኢህአዴግ ሲገባና ደርግ ሲበተን፣ ጊሽ ዓባይ ኪነት የመበተን ዕጣ ገጠመው፣ ስለዚህ የቡድኑ ዕቃ ነበር ተሸጦ ገንዘቡን ተከፋፈልነው፡፡ ሰው ሁሉ ይመክረኝ ጀመር። ‹‹እዚህ አገር ከሆንክ የማንም ጠላ ጠጪ አጫዋችና አጋፋሪ ሆነህ ነው የምትቀር እና ወደ መሃል አገር ሂድ›› አሉኝ፡፡ ስንከፋፈል የደረሰኝ 2ሺህ ብር ይዤ ‹‹አይን አፋር ሲሄድ አያፍር›› በሚባለው በሽንጣሙ አውቶብስ ተሰቅዬ ---በአይናፋሩ ስከንፍ አዲስ አበባ መጣሁልሽ፡፡ ዘመድ ነበረህ --- አዲስ አበባ? እኔ ነው?! እራ እንዴት ያለሽው ነሽ---- ከየት አምጥቼው፡፡ የአዲስ አበባ ዘመድ ደግሞ ሰው ሲመጣበት አይወድም፡፡ ገና ‹‹ሰላም መጣሽ›› ከማለቱ ‹‹መቼ ልትሄድ ነው የመጣኸው›› ነው የሚልሽ፡፡ ቤት ኪራይ ኑሮው እየመረረው ነው መሰል..፡፡ እብዛም ደግሞ ዘመድ የለኝም፡፡ የት አረፍክ ታዲያ? እራ እንደመጣሁ እማ.. ምን መሄጃ አለኝ፡፡ ያረፍኩት ጎጃም በረዳ አካባቢ ካለ ሆቴል ነው፡፡ በቀን ስምንት ብር እየከፈልኩኝ፡፡ ውድ ነው፡፡ ግን ስልክ ቁጥር ይዤ መጥቼ ነበር፡፡

ያን ጊዜ እነ ሰማኸኝ በለው፣ ይሁኔ በላይ፣ እነ አንሙቴ..የጊሽ ዓባይ ልጆች በሙሉ ወዲህ ዘልቀው ነበር። ብቻ ግን ‹‹..የሆነው ይሁን›› ብዬ ነው የመጣሁ፡፡ ወደ አዲስ አበባ ስመጣ፤ አንድ ነገር አስጠነቀቁኝ፡፡ ‹‹ዘንጦ፣ ሸልሎ፣ ሽክ ብሎ፣ ሱፉን ከረባቱን አድርጎ የምታየው ሰው ሁል ጤነኛ እንዳይመስልህ ሌባ ነው›› አሉኝ፡፡ ከአልቤርጎ እንዳልወጣ ሰፊ ነው ሃገሩ፡፡ ‹‹ብጠፋስ›› ብዬ የምውለው የምበላው እዚያው መኝታዬ አካባቢ ነው፡፡ አንድ ቀን ከአልቤርጎው አጠገብ ካሉ ሊስትሮዎች ጫማ እያስጠረኩ …የመኪና መለዋወጫ ስፔር ፓርት አለ፣ እሱ አጠገብ አንድ ሰው ቆሞ በአመክሮ ያየኛል፡፡ እንዴት ያለ የሸለለ መሰለሽ፡፡ እንዳ አጋጣሚ አቀርቅሬ ቀና ስል፤ አይን ለአይን እንገጣጠማለን፡፡ ቆየት ብዬ ቀና ስል፤ አሁንም አይን ለአይን እንገጣጠማለን፡፡ ‹‹አይ ሌቦ…ዋ!! እንዴት አድርጎ ነው የሚያየኝ፣ ሆዱን ለቅቶ›› .. በውስጤ እጫወታለሁ፡፡ ሲልስ ማጉረጥረጡን ያበዛብኝ መሰለኝ፡፡

ተነሳሁና በስድብ አጥረግርጌ ‹‹አንተ ሞሽላቃ ሌባ…የእንጨት ሽበት፣ አሁን ይሄን ሽበት ይዘህ..አሁን ይሄን ሽበት ይዘህ ትሰርቅ…›› አልኩት። እንደ ምንሜና ለወጠኝ፡፡ ሰውዬው እንደ መደንገጥ አለ። ሰው ተሰበሰበ.. ‹‹ምን ሆነህ ነው፤ ምን ሆነህ ነው›› እያሉ ጠየቁኝ፡፡ ‹‹ዋ አፍጦ እያየኝ..ምን ይሄማ አላወቃችሁትም እንጂ ሌባ እኮ ነው›› እያኩ እደነፋልሻለሁ፡፡ ሰው መደናገሬ ስለገባው ‹‹እረ እሻ…እረ እሻ..ሰውዬው የቆምክበት የስፔር ፓርቱ ባለቤት ነው›› ብለው ሲሉኝ ወከክ ብዬ ቀረሁልሽ፡፡ ዱላ ቀመስካ--- እረ!! ባለማዋቄ ተገርመው፣ አዝነው እንዴውም..ተሳስቀው ዝም አሉኝ፡፡ አንድ ቀን እዚያ ጎጃም በረንዳ የኪነት ጓዴን አንሙቴን አገኘሁትና አወጋን፡፡ በቃ እኔ ቤት ልከራይልህ ብሎ ካሳንቺስ ይዞኝ መጣ፣ ወይ አገር …አዲስ አበባን እያደነቅሁ የከተማ ልጅ ሆንኩኝ፡፡ ስወጣ ስገባ አካባቢውን እየለመድኩት መጣሁ፡፡ ካሳንቺስ አካባቢ ያሉ የምሽት ክበቦች ማምሻዬን መዞር ጀመርኩ። ምሽት ቤቶች በር ላይ ቆሜ ሲዘፍኑ እሰማለሁ፡፡ ወደ ውስጥ አልገባም፡፡ ካሳንቺስ ዮርዳኖስ ሆቴል ፊት ለፊት ጥሩ ምግብ ቤት የሚባል ቤት ነበር፡፡

እሳቸው ቤት ሄድኩ..ዘበኛውን አስገባኝ ስለው፣ ‹‹ምን ታደርግ?››አለኝ ‹‹ከጎጃም ነው የመጣሁ፣ ባለቤቲትን ማግኘት እፈልጋለሁ፡፡ ዘፋኝ ነኝ ›› ስለው ‹‹በል መልካም ሰው ናቸው--- ግባ እና አናግራቸው›› አለኝ፡፡ ሳናግራቸው “በል እስቲ ከዘፋኞች ላገናኝህ” ብለው አገናኙኝ፡፡ ዘፋኞቹ ‹‹እስቲ ሞክር›› ብለው ሲሉኝ ሳቀነቅን.. “ዓይነተኛው መጣ” ብለው ደስ አላቸው፣ ያንን ምሽት በምሽት ክበቡ ስዘፍን አመሸሁ--- ሽልማቱ ሌላ ነበር፡፡ የራስህ ዘፈን ነበር? ‹‹አንቱየዋ›› የሚለው የይሁኔ በላይን ነው፡፡ እራ እነዛ ‹‹ሞክር ዝፈን እስቲ›› ያሉኝ እኮ እያላገጡ ነበር። በደንብ እምሰራው አልመሰላቸውም ነበር፡፡ ሽልማቱ ቢዥጎደጎድልኝ ‹‹እረ እንዴት ነሽ ገንዘብ›› አልኩኝ፡፡ ገንዘቤን ተቀብዬ እግዚአብሄር ይስጥልኝ ብዬ ወጣሁ። በቤት ኪራይ ተወጥሬ ተይዤ ነበር…አከራዮቼን ባየሁ ቆጥር ነፍሴ ድርቅ እያለች ነበር፡፡ ሽልማቴን አግኝቼ ስመለስ ቀድሜ የአራት ወር የቤት ኪራይ ሁለት መቶ ብር ከፍያቸው ተገላገልኩ፡፡ ጥሩ ምግብ ቤት ተቀጠርክ? ወይስ--- እረ የለም፡፡ በቂ ሰው ነበራቸው፡፡ ይልቅስ ከጥሩ ምግብ ቤት አጠገብ ይሁኔ በላይና ሰማኸኝ በለው የሚጫወቱበት የምሽት ክበብ ነበር - ‹የሽዋ ጌጥ› የሚባል ..እነሱ በሃገር ባይኖሩም፡፡

ቦታውን ማወቄ አገር እንዳወቅሁ ---ደስ እያለኝ መጣ፡፡ ስል ስል እየለመድኩ በባህል ዘፈን ታዋቂ የሆኑ እነ አሸብር በላይ፣ ፋሲል ደሞወዝ፣ ጌቴ አንለይ …በሚሰሩበት የምሽት ክበብ ሌላ ስራ ሲኖራቸው እኔ የሚሰሩበት ቦታ እየተገኘሁ የእነሱን ቦታ መሸፈን…ጀመርኩ፡፡ በየትኛው የምሽት ክበብ ነው? ‹‹ከተፋ ቤት›› ይባላል፡፡ ድስትም ምጣድም አገልግሎት ከመስጠቱ በፊት በማባለቻ እንደሚሟሸው እኔም ራሴን በምሽት ክበቦች እያሟሸሁ ቆየሁ፡፡ እነሱ በሚሰሩበት ቦታ እየሄድኩ የነሱን ስራ ሽፈና ማለት ነው፡፡ የራስህን ካሴት አላወጣህም? አይ እናት አለም…አንድ ሞክሬ ነበር፤ ሳይሳካ ቀረ። አልተሸጠም፡፡ በአዲስ አበባ የባህል ምሽት ክበቦች እየተገኘሁ የባህል ዘፋኞችን ስራ ሽፈና ቀጠልኩ፡፡ ዛሬ ዛሬ ደግሞ ከባህል ዘፈኖች መሃል እየተሰነቀርኩ ራፕ ማድረግ…ማሽቃበጥ በይው---- እሰራለሁ፡፡ የከተማ ሰዎች ‹‹ራፕ የሚያደርገው---አሽቃባጩ-- ፋርኛው ራፐር›› ይሉኛል፡፡ የገጠሩ አድማጭ ደግሞ ‹‹አዳማቂው›› መጣ ይላል፡፡ አድማቂ ቢባል ይሻላል፡፡ አሽቃባጩ ማለት እኮ..አድርባይ አይነት ይሆናል..ሞያ ነው--- የህዝብ ባህል ነው፣ ማክበር እፈልጋለሁ፡፡ በአዳማቂነት ለመጀመርያ ጊዜ በካሴት የሰራኸው ከማን ጋር ነው? በማናልቦሽ ዲቦ ዘፈን ነው ለመጀመሪያ ጊዜ የሰራሁት፡፡ ስቱዲዮ ተጠርቼ ተቀረፅኩኝ ‹‹ሆይ መላ ነሽ አሉ ሆይ መላ›› ብላ ስትዘፍን እኔ ‹‹አለው መላ መላ›› ብዬ ሙዚቃውን ልቀበል ነበር የሄድኩት፡፡

ስቱዲዮ ውስጥ ገብቼ ኤርፎኑን ጆሮዬ ላይ ካደረኩኝ በኋላ ….አንድ ሃሳብ መጣልኝ… ‹‹ጠላው ተደርጎ፣ ቡናው ተፈልቶ፣ ዘመድ ተጠራርቶ፣ እንዲያ ነው ዓመት በዓል›› እያልኩ ስጨማምር…በጣም ወደዱት፡፡ በዚያው ይሄው ከሁለት መቶ በላይ ዘፈኖች ላይ ከታዋቂዎች እስከ ጀማሪዎች የባህል ዘፋኞች አድማቂ ለመሆን ቻልኩ፡፡ ከዛ በኋላማ ለቁጥር በሚያታክቱ የጎጃም፣ ጎንደር፣ወሎ ..እነ አቤል ሙሉጌታ፣ ማዲንጎና ብሩሃኑ ተዘራ “አንበሳው አገሳ”--- ገነት ማስረሻ፣ ግዛቸው፣ ብርቱካን ዱባለ --- ምን ልበልሽ…. ዘመናዊውን አልነካሁም እንጂ--- በባህል ዘፈን ላይ ግን አድማቂው--- የባህል ሙዚቃ ራፐሩ እኔ ነኝ፡፡ ልዩ ትምህርት ወይም ተሰጥኦ ይጠይቃል? እራ.. በገጠር የባህል ዘፈን ውስጥ እኮ ያለ ነው። አንዱ ሲያቀነቅን --- አንዱ ያዝ፣ ተቀበል፣ ውጣ፣ ውረድ፣ እንደዚህ አርገው፣ ወይ ጥጋብ፣ ወይ አመል፣ ያዝ፣ ተቀበል---- ሲል ነው የሚደመጥ፡፡ በጎጃም ብትይ በጎንደር..ከባንድ በላይ እኮ የሰርግ ዘፈን በገጠር ይደምቃል፡፡ በሰርግ፣ በጥምቀቱ እንዘፍናለን..ሰርግ ጥሪ ስንገኝ እየተበላ፣ እየተጠጣ፤ ፉከራ ነው፣ ማቀንቀን ነው---- ሌላ ነው አልኩሽ፡፡ እኔ ከሙዚቃ ጋር ቅኝቱና ንግግሩ እንደዜማ ሆኖ በሙዚቃው ውስጥ እንዲሆን ነው ያደረኩትኝ፡፡ ያ ነው ለየት የሚያደርገኝና ወደ ፈጠራ የሚያመጣኝ፡፡ ቃሎችን እራሴ ፈጥሬ፣ ዘፈን ሰምቼ --- ዘፈንን የማቃናት ስራ ነው የምሰራው፡፡

ሙዚቃውንና ዘፈኑን እሰማለሁ እና ርዕሱን አያለሁ--- ሊል የፈለገው ምንድን ነው የሚለውን አዳምጬ፣ ያልተቃናውን ማቃናት፤ ድብስብስ ያለውን ደግሞ የመግለፅ ስራ ነው የምሰራው፡፡ “እሰይ መጣልን አውዳመት ..እያለች” ስትዘፍን ማናልቦሽ ..እኔ ያሰብኩት “አውዳመት መሃል ምን አለ?” የሚለውን ነው፡፡ ዘመድ ይጠራራል፣ ጠላው፣ ቡናው፣ ዳቦው…ይሄንን ነው፡፡ ይሄው እንዳዳመቅሁ እንዳሽቃበጥኩ አለሁ፡፡ ግን መብያ አድርጎልኝ እግዚሃቤር.፡፡ አንድ በጣም የሚከፋኝ ነገር አለ፡፡ እንደዚህ ለባህሉ ሙዚቃ ማማር እየሰራሁ---- ለሞያው ክብር ያለመስጠት ይሁን ሌላ…በሙዚቃው ውስጥ ከካሜራ ማን እስከ…አልፎ ሂያጁ ድረስ ስምና ማንነት ሲጠቀስ --- በክሊፕም ሆነ በካሴት “አድማቂ ጥጋቡ ቸርነት” ብለው ገልፀው አያውቁም፡፡ በአንድ ዘፈን ለአድማቂነት ስንት ይከፈልሃል? አይ እሱ ነው አበሳው…በነፃ ከመስራት ጀምሮ፣ እስከዛሬ ትልቁ ስድስት መቶ ብር ነው የተከፈለኝ፡፡ መተዳደሪያህ ይሄው ነው? ከማሽቃበጡ በተጨማሪ በሸዋጌጥ፣ በአይቤክስ፣ በሁለት ሺህ አበሻና በብዙ ናይት ክለቦች ውስጥ ሰርቻለሁ።

አሁን ደግሞ ደሳለች ክትፎ፣ ቦሌ ነው የምሰራው… ሰርጎች ላይ የተለያዩ የባህል ስራዎች እሰራለሁ፡፡ ያለ አንተ አዳማቂነት የተሰሩ ዘፈኖችን ሰምተህ እዚህ ቦታ ላይ እኔ ብኖር ኖሮ ያልክበት አጋጣሚ አለ? በጣም በርካታ እንጂ--- ክፍተት ከመሙላት ጀምሮ እስከ ልዩነት ማምጣት ድረስ፡፡ አንዳንዴ አለመገጣጠም ይሆንና አያስቡትም፡፡ አንዳንዴ ለአንድ ዘፈን የተቀረፅኩትን ለሌሎች ድምፃውያን አስገብተውት አገኛለሁ፡፡ ይህችም እንጀራ ሁና!! እንደ ኮፒ ራይት ጥሰት አስቢው፡፡ መጥታ እንኳን ጉሮሮ የማታረጥብ…ይሄ በጣም እየረበሸኝ ነው፡፡ ለምን መሰለሽ በጣም እየተለመድኩ መጣሁ፡፡ በገጠር ‹‹እኛ ሽማግሌ የሌሉበት ሙዚቃስ አይደምቅም›› ይላሉ፡፡ ሸመገልክ እንዴ ጥጋቡ እስቲ ዕድሜዬን በአይተሽ ሙይው እንዳላሳንስብህ አንተ ንገረኝ እርግጡ 30 ዓመቴ ነው፡፡ ትዳር፣ ልጆች? ሶስት ልጆች አሉኝ፣ አግብቻለሁ፡፡

Published in ጥበብ
Saturday, 04 May 2013 13:48

ባቡሩ ሲመጣ

አይነ ስውሩ ለማኝ የሰሙትን ነገር ለማመን ቸግሯቸዋል፡፡ በቀኝ መዳፋቸው የያዟቸውን ሳንቲሞች በቀስታ እያሻሹ ጥቂት ሲያስቡ ቆይተው፣ ከበስተቀኛቸው ቁጭ ወዳሉት ወደ እማማ እቴናት ዘወር አሉ፡፡ “የማነው ስሙ …የጌትዬ ሱቅስ?” በጉጉት ተውጠው ጠየቁ፡፡ “የእሱም ፈርሷል” እማማ እቴናት ከፊታቸው የዘረጉትን የነተበ የምጽዋት ምንጣፍ እያስተካከሉ መልስ ሰጡ፡፡ “ተውራየል ግርጌ ያለው…የዚያች የጐንደሬይቱ ውቴልስ?” ቀጠሉ ሰውዬው፡፡ “ኤዲያ!.. ‘ተላይ እስተታች አፍርሰውታል’ እያልሁዎት አይሰሙኝም እንዴ?” በተሰላቸ ድምጽ መለሱላቸው፡፡ አይነ ስውሩ በሀዘኔታ አናታቸውን እያወዛወዙ በሃሳብ ተዋጡ፡፡ ስጋት ገብቷቸዋል፡፡ እየሆነ ያለው ነገር ግራ አጋብቷቸዋል፡፡ “እንዲያው ግን…ምን ይሁን ብለው ነው አሉ አንቺዬ?” አይነስውሩ አገጫቸውን ሽቅብ ሰቅለው ጠየቁ። እማማ እቴናት በአይነስውሩ ጥያቄ በመሰላቸት፣ በረጅሙ ተንፍሰው ፊታቸውን ወደ ባምቢስ አቅጣጫ አዞሩ፡፡

“ሰማሽ ወይ?” ሰውዬው በጥርጣሬ ወደ እማማ እቴናት ዞረው ጠየቁ፡፡ “ሴትዬዋ መልስ አልሰጡም፡፡ ከኡራኤል አቅጣጫ የሚመጡ ጋቢ የለበሱ አዛውንት የተመለከቱና ጉሮሮዋቸውን አጽድተው መለመን ቀጠሉ፡፡ “ስለአዛኝቷ…ስለ ኪዳነ ምህረት…” አሉ በሚያሳዝን ዜማ፡፡ አዛውንቱ ኪሳቸውን ፈትሸው ያገኟቸውን ዝርዝር ሳንቲሞች የእማማ እቴናት ጨርቅ ላይ ጣል አድርገው አለፉ፡፡ “ኪዳነምህረት ትስጥልኝ… የነፍስ ዋጋ ያርግልኝ!” ዜማ ቀይረው መመረቅ ጀመሩ - እማማ እቴናት፡፡ አይነስውሩ የባልቴቷን ምርቃት ለማስጨረስ የሚሆን ትዕግስት አልነበራቸውም፡፡ “እኔ እምልሽ…ምን ይሁን ብለው አሉ…እንዲህ አገር ምድሩን ያፈራረሱት?” ጣልቃ ገብተው ጠየቁ፡፡ “ባቡር ሊተክሉ ነው አሉ!” ሲሉ መለሱ እማማ እቴናት፤ ጨርቁ ላይ የተዘሩትን ሳንቲሞች በአይናቸው እየደመሩ፡፡ “ኧረ አንዳች ውጋት ይትከልባቸው!” ቆጣ ብለው ተናገሩ አይነ ስውሩ፡፡ እማማ እቴናት በሰውዬው ንግግር በድንጋጤ ክው ብለው በስጋት ዙሪያቸውን ተገላምጠው ተመለከቱ፡፡ አለፍ ብለው ታክሲ እየጠበቁ ከቆሙት ሰዎች በስተቀር፣ የአይነስውሩን ንግግር ሊሰማ የሚችል ሰው በዙሪያቸው አለመኖሩን ሲያረጋግጡ ስጋቱ ቀለል አለላቸው፡፡

ይሄም ሆኖ ግን የአይነ ስውሩን አጉል ንግግር ዝም ብለው ማለፍ አልፈለጉም፡፡ “እስዎ ሰውዬ…ይሄን አጉል ንግግር ቢተው መልካም ነው፡፡ ምን ባረጉ ነው እሚረገሙ? አገር ላልማ ባሉ አጉል መናገር ምንድነው? …” ብለው ጀመሩ፡፡ አይነስውሩ በቁጣ ቱግ ብለው አቋረጧቸው፡፡ “ኤዲያ!...አንቺ ደሞ እምኑ ላይ ነው ንግግሬ አጉል እሚሆነው?...” ሳንቲሞቻቸውን ወደ ኮት ኪሳቸው እየጨመሩ ኮስተር ብለው ተናገሩ፡፡ እማማ እቴናት አለፍ ብሎ የቆመ የታክሲ ወያላ ዝርዝር ሳንቲም ፍለጋ ላይ መሆኑን አይተው በፍጥነት ከተቀመጡበት ተነሱ፡፡ በአይናቸው የደመሯቸውን ዝርዝር ሳንቲሞች ይዘው ሄደው፣ አራት ድፍን ብሮች ይዘው ሲመለሱ የአይነስውሩ ዝርዝር ወግ ጠበቃቸው፡፡ “ውነቴን እኮ ነው?...ምን እንዳይመጣ ነው?” አይነስውሩ ንግግራቸውን ገታ አድርገው የእማማ እቴናትን መልስ መጠባበቅ ጀመሩ፡፡ “የሚመጣውንማ ያዩታል! ምን ማለትዎ ነው?…ልማት እኮ ነው! ስንቱ ባለሱቅ ሸቀጡን ሸካክፎ ያንን የመሳሰለውን ህንጣ “እሺ” ብሎ ያፈረሰው፣ የሚመጣበትን ቢያውቅ አይደለ እንዴ?” የባልቴቷ ንግግር በአይነስውሩ ድንገተኛ ሳቅ ተሸፈነ። “አይ አንቺ… ‘ተናት ትበልጥ ሞግዚት፣ ታንቃ ትሞት’” አሉ… ሳቃቸውን ገታ አድርገው፡፡

እማማ እቴናት በአይነስውሩ ሳቅ ክፉኛ ተበሳጩ። ከሳቁ ውስጥ እንደ ንቀትም፣ እንደ ሽሙጥም፣ እንደ ስላቅም የሚመስል ነገር ሰምተዋል። “ሰማሽ ወይ…እኔና አንቺ ተዚህ የባሰ ምን ይመጣብን ብለሽ ነው እንዲህ እምትባትቺው… እንጥፍጣፊ ሳቅ ፊታቸው ላይ ይታያል፡፡ …እንኳን እኛ፣ ስንቱ ባለጠጋ ከቦታው ተነስቶ የለ እንዴ?...ደሞስ “ለልማት ተሆነ…” ባልቴቷ መቀጠል አልቻሉም፡፡ አይነስውሩ በቁጣ ቱግ ብለው የተቀመጡበትን ቅዳጅ ካርቶን እየነካኩ ወደ ባልቴቷ ዘወር አሉ፡፡ “ያነዜማ ይለይልናል..በገዛ አገሬ “ለምነህ አትበላም” ተባልኩማ ጉድ ይፈላል” እንደ መፎከር አደረጋቸው፡፡ ባልቴቷ በተራቸው የአይነስውሩን የሚመስል እንደ ንቀትም፣ እንደሽሙጥም ያለ ሳቅ አመለጣቸው። “እንዴት?” የሰውዬው ንዴት ከመንግስት ወደ ባልቴቷ ዞረ፡፡ “ተናግሬያለሁ!…እነሱ እንደሆኑ በልማቱ ለመጣባቸው ፊት አይሰጡም…አጉል አጉል ሲናገሩ ጉድ እንዳያፈሉ” ከወያላው የተቀበሉትን ብር ወደ ከረጢታቸው እየከተቱ ተናገሩ፡፡ “በይሆት ይሆኑ እያለሁ ተዚች ቦታ የሚያስነሳኝ ሰው ተተገኘ እውነትም እናቱ ወልደዋለይ” ይኸው እሱ ይታዘበኝ… ወደ ኡራኤል ቤተክርስቲያን አቅጣጫ እየጠቆሙ በእልህ ተናገሩ፡፡ “ኧረ ይተው፣ እንደ አፍ አይቀናም” ባልቴቷ የከረጢታቸውን ሸምቀቆ አጠበቁ፡፡ አይነ ስውሩ የባልቴቷ ንግግር ንቀት እንዳለበት ለመገንዘብ ጊዜ አልፈጀባቸውም፡፡ ጊዜ የፈጀባቸው፣ ምን ብለው መልስ እንደሚሰጡ ማሰቡ ነው፡፡ እርግጥ ነው፣ የሴትዬዋ ንቀት ደማቸውን አፍልቶታል፡፡ ይሄም ሆኖ ግን፣ “ደሜ ፈላ” ብሎ በግልፍተኝነት አጉል መልስ መስጠት የሴትዬዋን ውለታ ብቻ ሳይሆን፣ ንግግሩ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋም መዘንጋት ይሆናል፡፡

አይነስውሩ የባልቴቷ ውለታ አለባቸው፡፡ ከዋናው አስፓልት ዳር የሚገኘው ይህ የተቀመጡበት ቦታ፣ ለእማማ እቴናት እንጂ ለሌላ “የኔ ቢጤ” የተከለከለ ነበር። እርግጥ ማን እንደከለከለ በውል አይታወቅም፡፡ እማማ እቴናት እዚህ ቦታ ላይ ተቀምጦ ለመለመን የሞከረን የኔ ቢጤ፣ በግልምጫም በፍጥጫም ነዝንዘውና አስፈራርተው በማባረር ለረጅም ጊዜያት ቦታውን የራሳቸው ግዛት አድርገውት ኖረዋል፡፡ አንዳንድ የኔ ቢጤዎች “እሷ እኮ የመንግስት ጆሮ ጠቢ ናት” በማለት ያስወሩባቸዋል፡፡ እርግጥ ሃሜቱን የፈጠረው የራሳቸው የእማማ እቴናት ሁኔታ ነው፡፡ አንዳንዴ እንደ ፖለቲከኛ ያረጋቸዋል፡፡ “እድሜ ለእነሱ…ይሄው ሰላም ውለን እንገባለን!!...አዳሜ አይንሽ በቅናት ይቅላ እንጂ እነሱ እንደሆኑ ማልማታቸውን አይተውም” ይላሉ፣ “እነሱ” እነማን መሆናቸውን ሳይገልፁ በደፈናው፡፡ እንዲህ ያለው “ልማታዊ” ንግግራቸው ነው፣ “ነገር አላቸው” ብሎ የሚያሳማቸውም፣ የሚያስፈራቸውም፡፡ አንድ ወቅት ግን አይነ ስውሩ ለማኝ ድንገት ከካንቺስ አቅጣጫ መጡና ከእማማ እቴናት ጋር ወግ ጀመሩ፡፡ እማማ እቴናት ስለ ልማቱ ያወሯቸውን በጐ በጐ ነገር ሁሉ እየተቀበሉ “ልክ ነሽ” ሲሏቸው ቆዩ፡፡ እንደዋዛ ከጐናቸው ቁጭ ብለው እያወሩ እግረ መንገዳቸውን ሲለምኑ ዋሉ። እማማ እቴናት አይነስውሩን ወደዷቸው፡፡ በነጋታውም እዚያው ቦታ ላይ እንዲለምኑ ፈቀዱላቸው፡፡ አይነስውሩ ይህን ውለታ አፍርሰው “ለምን ናቅሽኝ” ብለው ፀብ መግጠም አልፈለጉም፡፡ ከእማማ እቴናት ጋር መጋጨት፣ ከባቡሩ ጋር መጋጨት እንደሆነ ገብቷቸዋል፡፡ ከባቡሩ ጋር መጋጨት ደግሞ ከልማቱ ጋር መጋጨት ነው፡፡ አይነስውሩ በሃሳብ ተውጠው መተከዝ ጀመሩ፡፡

“እኔ እምልሽ እቴናት…?” አሉ አይነስውሩ በውስጣቸው ሲመላለስ ለቆየው ጥያቄ መልስ ባገኝ ብለው በማሰብ፡፡ “አቤት” እማማ እቴናት በሰለለ ድምጽ መለሱ፡፡ “ምን ይሁን ብለው ነው፣ ይኸን ሁሉ ቤት ያፈራረሱት አሉ?” “ዘነጉት እንዴት? ‘ባቡር ሊተክሉ ነው አሉ’ ብየዎትም አልነበር?” የተሰላቸ ምላሽ ሰጡ፡፡ “እ…እሱስ አልዘንግቼውም እንዲያው ብቻ…ላንድ ባቡር ይሄን ታህል አገር መፍረሱ ገርሞኝ ነው… እስተ ላይ ድረስ ነው አሉ ያፈራርሰውት” በመገረም መልሰው ጠየቁ፡፡ “እህሳ” አረጋገጡላቸው፡፡ አይነስውሩ ግራ በመጋባት ጥቂት ሲያስቡ ቆዩ። ዋናውን አስፓልት ተከትሎ ግራና ቀኝ የነበሩ በርካታ የንግድና የመኖሪያ ቤቶች “ለባቡር ግንባታ” በሚል የመፍረሳቸው ነገር እንቆቅልሽ ሆኖባቸዋል፡፡ “ቆይ…አንድ ባቡር ለመትከል ይኸን ሁሉ ቤት ማፍረሳቸው ምን ባይ ነው?” በማለት ወደ እማማ እቴናት ጥያቄያቸውን ሰነዘሩ፡፡ “እኔ ምኑን አውቄ ብለው ነው” አሉ እማማ እቴናት ከበስተጀርባቸው ያሉትን ፍርስራሾች ዘወር ብለው እየተመለከቱ፡፡ “ደሞስ …እህል እንጅ ባቡር መች ቸገረን?…ያንድ የወንዳፍራሽ ባቡር አይደለ እንዴት፣ ይህን ያህል ዘበን የውራየልንና የካዛንቺስን ህዝብ ቀጥ አርጐ ያኖረው?” አይነስውሩ በመገረም ተናገሩ፡፡ እማማ እቴናት የአይነስውሩን አባባል ከፀረ -ልማት ትችት ቆጥረው ተገቢ ምላሽ ለመስጠት ሲዘጋጁ ቆይተው፣ ድንገት በሳቅ ፍርስ አሉ፡፡ “እንዴት?” የድንገተኛው ሳቅ ሰበብ ያልተገለጠላቸው አይነስውሩ ፈጠን ብለው ጠየቁ፡፡ “አይ እስዎ… ‘ባቡር’ ብልዎት፣ የህል ወፍጮ መስሎዎት ነው ለካ?” ያቋረጡትን ሳቅ ቀጠሉ፡፡ “እህሳ?…‘ባቡር ሊተክሉ ነው’ አላልሽኝም?” ግራተጋቡ ሰውዬው፡፡ “እሱስ ብዬዎት ነበር…” አሉና በእንጥልጥል ትተውት የቀረ ሳቃቸውን አሟጠጡ፡፡ “እና ምንድነው እሚያስቅሽ?” የተናደዱ ይመስላሉ፡፡

“አይ…ባቡር ስልዎት እኮ…የህል ወፍጮ ሳይሆን…” ብለው ጀመሩና አሁንም በእንጥልጥል ተውት፡፡ ምክንያቱም ይተከላል የተባለው “ባቡር” የእህል ወፍጮ አለመሆኑን እንጂ፣ “ምን” መሆኑን እርሳቸውም ቢሆኑ በእርግጠኝነት አያውቁም፡፡ ከእሳቸው አለፍ ብለው ጫማ ሲጠርጉ የሚውሉት ወጣቶች ሲያወሩ የሰሙት፣ ‘ባቡር’ የሚባል ተሽከርካሪ” ሊመጣ መሆኑን ብቻ ነው። እርግጥ እማማ እቴናት በወሬም ቢሆን ከሰውዬው የተሻለ ስለጋቡር ግንዛቤ አላቸው፡፡ ባቡር የመሳፈር እድል ባያገኙም፣ ሀዲድ የመሻገር አጋጣሚ ነበራቸው፡፡ የቂርቆስን በአል ጠብቀው ስራ ፍለጋ ሲያቀኑ የሚሻገሩትን ሀዲድ ‘የምን እንቅፋት ነው?’ ሲሉት ኖረው፣ አንድ እለት የባቡር መንገድ መሆኑን ሰው ነግሯቸዋል፡፡ “እህ…እንዴት ያለ ባቡር ነው ዛዲያ?” ግራ ተጋብተው ጠየቁ ሰውየው፡፡ እርግጥም ግራ መጋባት ሲያንሳቸው ነው፡፡ ለእሳቸው “ባቡር”፣ የእህል ወፍጮ ነው፡፡ ከእህል ወፍጮ በቀር “ባቡር” የሚባል ነገር ስለመኖሩ የሚያውቁት ነገር የለም። ገጠር ተወልደው ገጠር ያደጉ ገበሬ ናቸው (ይቅርታ ‘ነበሩ’)፡፡

ግብርናው አልሆን ብሏቸው ከ2 አመታት በፊት ወደ አዲስ አበባ ሲመጡም በኤነትሬ እንጂ በባቡር ተሳፍረው አልነበረም፡፡ “እንጃ እኔ…ብቻ እንዲያው…’እንደ መሂና ያለ ነው’ አሉ… ሰው እሚያመላልስ” አሉ እማማ እቴናት፣ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዳይጠየቁ በመስጋት ነገሩን አድበስብሰው ለማለፍ፡፡ የፈሩት ደረሰ፡፡ የአይነስውሩ ጥያቄ ከጆሯቸው ደረሰ፡፡ “ወይ ታምረ ነገር…ይኸ ሁሉ መሂና ሞልቶ፣ ምን እሚሉት “ባቡር” ነው እሚተክሉ?” በመገረም ጠየቁ አይነስውሩ፡፡ እማማ እቴናት ከጥያቄው ለመሸሽ አይኖቻቸውን ወደ መንገደኛው መለሱ፡፡ “አትለፉኝ ወገኖቼ…ተዘከሩኝ…ባዛኝቷ!...” ሳንቲሞቻቸውን እያንቃጨሉ በሚያሳዝን ዜማ ልመና ጀመሩ፡፡ አይነስውሩ በሰያፍ ይዘው በጥርሳቸው ሲሞርዷት የቆዩዋት ሳንቲም ሽልንግ መሆኗን ካረጋገጡ በኋላ ወደ እማማ እቴናት ዞር አሉ፡፡ ‘እንደ መሂና ያለ ነው’ አልሽኝ?” በመገረም፡፡ “ሊስትሮዎይ እንዲያ ሲሉ ነበር” በመሰላቸት፡፡ “የሆነውስ ሆኖ…እንዲያው ግን…ይኸ ባቡሩ ምን ያህላል አሉ? አሉ ሰውዬው ጥቂት ሲያስቡ ቆይተው፡፡ እማማ እቴናት በስም እንጂ በአካል የማያውቁትን ባቡር መጠን ለመገመት ተቸግረው ጥቂት ሲያሰላስሉ ቆዩና፣ ከዋናው አስፓልት ማዶ የፈረሱ ቤቶችን እያዩ መለሱ፡፡

“መቸም ተዚህ ተትልቁ አውቱቢስ ሳይበልጥ አይቀርም” የራሳቸውን ግምት ሰጡ፡፡ “ውራየል አውጣኝ!” በማጋነን ጮህ ብለው ተናገሩ፤ ሰውዬው፡፡ “እንዴት?” ሴትዬዋ በግምታቸው እንደማፈር አሉ፡ “ያንት ያለህ?” አይነስውሩ አናታቸውን በግርምት እየወዘወዙ ለራሳቸው አወሩ፡፡ “መቼም…ታውቱቢሱ ባይተልቅ ይኸን ያህል መንደር አፍርሰው መንገድ አይጠርጉለትም ነበር” ግምታቸውን በመረጃ ለማስደገፍ ሞከሩ፡፡ “ጉዳችን ሊፈላ ነዋ?” ድምፃቸው ውስጥ ስጋት አለ፡፡ “ኤዲያ!...ይኸን መቀባጠር ሞያ ብለውት!...አገር ሲለማ ጉድ የሚፈላው ተመቼ ወዲህ ነው?” ባልቴቷ ልማታዊ ቁጣ ተቆጡ፡፡፡ “ይኸ ባቡሩ ታውቶቢሱ ተተለቀማ ጉድ ፈላ” የባልቴቷን ምላሽ ለመስማት ጓጉተዋል፡፡ “እስዎ ደሞ እድሜ ልክዎን ልማቱን እንዳሽሟጠጡ ነው!...እናታለም አትለፊኝ…የኔናት ለነፍስሽ ብለሽ ተዘከሪኝ…” ከሰውዬው ወደ ወጣቷ ዞሩ - ወደ ታክሲ ፌርማታው ስትጓዝ ወዳዩዋት፡፡ ወጣቷ ምላሽ ሳትሰጣቸው አለፍ ብለው ታክሲ ከሚጠብቁ ሰዎች ጋር ሰልፍ ያዘች፡፡ “ሰማሽ ወይ?...ይኸ ባቡሩ ትልቅ ተሆነማ ሺ ተምንተሺ ሰው ማሳፈሩ አይቀርም?...” በስጋት ተውጠው ጠየቁ አይነስውሩ፡፡ “አንቱዬ…ዛሬስ ደናም አይደሉ መሰል? አጉል ወግ ሲጠርቁ ስንቱ መንገደኛ አለፈ!...ምናለ ልማቱን ማሽሟጠጥ ትተው ስራዎን ቢሰሩ?” ቆጣ ብለው፡፡ አይነስውሩ የፌዝ ሳቅ አሰሙ፡፡

“አይ እቴናት… ‘አጉል ወግ’ አልሽው?...አንቺ መቼ ነገሩ ገብቶሽ? ‘መንገደኛው ሳይሰጠኝ አለፈ’ ብለሽ ትብከነከኛለሽ?...አይ ሞኚት…ይኸ ባቡር እሚሉት ነገር መጥቶ አዳሜን ጠራርጐ እያጐረ ይዞት ሲነጉድ፣ ኸትኛው መንገደኛ እንደሚዘከርሽ ታያለሽ!” ብለው ጆሯቸውን ወደ መንገዱ ቀሰሩ፡፡ እማማ እቴናት ይሄን ንግግር ሲሰሙ ድንገተኛ ስጋት ተፈጠረባቸው፡፡ የአይነስውሩ ንግግር እሳቸው እንዳሰቡት “አጉል ወግ” አለመሆኑ ተሰማቸው። “ይመጣል” የተባለው ባቡር የእለት እንጀራቸውን ከፊታቸው ጠራርጐ ይዞ ወደ ሩቅ መንደር የሚሄድ ጠላታቸው ሆኖ ታያቸው፡፡ መንግስት በከተማዋ ያለውን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ በማሰብ የሚተክለው ባቡር፣ መንገደኛውን በሙሉ አጭቆ ይዞ ሲከንፍ፣ እዚህ ቦታ ላይ ታክሲ ጠባቂ ሰው አይኖርም፡፡ የታክሲ ፌርማታው ጭር ይላል፡፡ “ለነፍሴ” ብሎ እሚመፀውት ሰው ይጠፋል፡፡ ከበስተቀኛቸው አለፍ ብሎ ተሰልፎ ታክሲ የሚጠብቀው ይሄ ሁሉ መንገደኛ፣ ባቡሩ ሲመጣ እዚህ ቦታ ላይ ላይኖር ይችላል፡፡ ታክሲ ጠባቂ መንገደኛ ከሌለ ደግሞ መጽዋች አይኖርም…እሳቸው የሚኖሩት ደግሞ መፅዋች ሲኖር ብቻ ነው፡፡ እማማ እቴናት ስጋት ገባቸው፡፡ የህልውና ስጋት!

Published in ልብ-ወለድ

የአፍሪካ ህብረት የተመሠረበትን 50ኛ አመት ምክንያት በማድረግ በቻቺ ኢንተርናሽል አርቲስት ማናጅመንት የተሰናዳ የአፍሪካ ሙዚቃ ፌስቲቫል ግንቦት 3 እና 4 በሚሊኒየም አዳራሽ ይቀርባል፡፡ በአርቲስት ቻቺ ታደሠ በሚመራው ዝግጅት ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰባት የአፍሪካ ሃገራት የተውጣጡ ሙዚቀኞች ተሳታፊ እንደሚሆኑ አዘጋጆቹ በጋዜጣዊ መግለጫቸው አስታውቀዋል፡፡ አርቲስት ቻቺ ታደሰ፤ ዝግጅቱን እንዲያደምቁ የ40 አገራት አርቲስቶችን ለመጋበዝ ብትሞክርም በኤምባሲዎች ትብብር የተሳካው የስድስት ሀገራት መሆኑንና ሂደቱ አድካሚ እንደነበር አመልክታለች፡፡

በዝግጅቱ ላይ ከኢትዮጵያ ሃይሌ ሩትስ እና ቺጌ ባንድ እንዲሁም ቻቺ ራሷ “I am an African” የሚለውን ዘፈኗን በመዝፈን ተሣታፊ እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡ ለሁለት ተከታታይ ቀናት የሚካሄደውን የሙዚቃ ዝግጅት ፌስቲቫል ለመታደም ከጠዋቱ 3-12 ሰዓት ለሚቀርበው ለአዋቂዎች 50 ብር፣ ለህፃናት በነፃ ሲሆን ለምሽት የሙዚቃ ዝግጅቶች ለአንድ ሰው መግቢያ የ200 ብር ቲኬት መዘጋጀቱን አስተባባሪዎቹ አስታውቀዋል፡፡

የበይነ መረብ (internet) አጠቃቀምን አስመልክቶ የተዘጋጀው መጽሐፍ ለንባብ በቃ፡፡ በዓለም ደገፋ እና ወንድወሰን አሰፋ የተዘጋጀው “በይነመረብ” የተሰኘ መጽሐፍ በዘርፉ ያሉትን የእንግሊዝኛ ቃላትና ሐረጐች በአማርኛ ቃላት ለመተካት የተሞከረበት ነው፡፡ አስራሰባት ምእራፎች ያሉት መጽሐፍ በበይነመረባዊ የቃላት መፍቻ የታገዘ ነው፡፡ ከ185 ገፆች በላይ ያሉት መጽሐፍ በ50 ብር እየተሸጠ ነው፡፡

Page 11 of 14