Tuesday, 14 April 2015 08:15

ትንሳኤ

ልጄን ሌላ ሆቴል ውስጥ አስቀምጨ ነው የመጣሁት። ሰዓቱ ከመሸ ብደርስም ግቢው በግርገር እንደተሞላ ነበር። ሰራተኞቼ ሙሉ ጊዜያቸውን ሰጥተው ዝግጅቱን አጧጡፈውታል፡፡
“ዋው! ጥሩ ሰዓት ደረሳችሁ! ባቢስ?” ሃላፊው እየሳቀ መጥቶ ጨበጠኝና ሻንጣየን ከሹፌሩ ጋር ማውረድ ጀመረ። ህንጻው ዙሪያውን  በተለያዩ ዲኮሮች አጥሩ በባንዲራ አጊጧል፡፡ ምስቅልቅል ያለ ስሜት እየተሰማኝ እዛው ቆሜ ትንሽ ካየሁ በኋላ ወደ ውስጥ ገባሁ፡፡ በስመአብ! ይበልጥ የደመቀው ትልቁ አዳራሽ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ያላየሁት እስኪመስል እዛው ቆሜ ቀረሁ፡፡ ሙሽራ ሊቀበል የተዘጋጀ ነው የሚመስለው፡፡ ለነገሩ ለእኔ የነገዎቹ እንግዶች ከምንም ሙሽራ በላይ ናቸው፡፡ በተለይ ባብዬ! አምላክ በዚህ ሁሉ አውጥቶ ለዚህ አበቃልኝ፡፡ እና ከዚህ በላይ ምን ሙሽራ አለኝ? አዎ! ነገ ከእኔና ከልጄ በላይ ሙሽራ የለም፡፡ ብዙ ታላላቅ ሰዎችንና ባለስልጣናትን ብንጠራም፣ ሙሽራዎቹ ግን እኛ ነን፡፡ የምናምር፣ ሌላ ተጓዳኝ ያልጨመርን እናትና ልጅ ሙሽሮች፡፡ ለነገሩ ለማያውቅ ሰው የእውነት ባልና ሚስት ነው የምንመስለው፡፡ ባብዬ ሰውነቱ ግዙፍ ስለሆነ አንድም ሰው እናትህ ብሎት አያውቁም፡፡ ቀረብ ያላሉ ጓደኞቹ ሁሉ እህትህ እያሉ ነው የሚጠሩኝ፡፡
ተፈጥሮዬ አጭር ባልባልም ብዙ ነገሮችን የተሸከምኩበት አካሌ የባቢ እናት ለመባል የሚያበቃ ግዝፈት የለውም፡፡ ለነገሩ በእድሜም ቢሆን የምበልጠው አስራ አራት አመት ብቻ ነው፡፡ ባብዬ የመጀመሪያ ልጄ ነው፡፡ ምን መጀመሪያ፤ መጨረሻም እንጅ! ከእሱ አባት ወዲህ ወንድ!... በማለቴ ልጄም አንድ ብቻውን እንዲቀር ፈርጀበታለሁ፡፡ ለባቢ አባት የነበረኝ ፍቅርም ሆነ ደግነቱ አልነበረም ከሱ ሌላ ያሰኘኝ፡፡ ወላጆቹና ወላጆቼ ተነጋግረው ያጋቡን ገና በስምንት አመቴ ነው፡፡ ከዛ የሚያጋጥመኝ አቀባበል ብቻ ሳይሆን ከእናቴ መለየቴ ጭምር ከብዶኝ በየጊዜው መኮብለል ሥራዬ ሆነ፡፡ እሱ ደግሞ እንደልጅ ከማባበል ይልቅ እየተከታታለ በመግረፍ አሰቃየኝ፡፡
ወላጆቼም በርበሬ አጥነውና ገርፈው ስላልቻሉ “እንግዲህ ሰው ልጁን አይገድል! ካልሆነ ትቅርብህ እንጅ ማለት ጀመሩ፡፡ በዚህ ላይ እንዳለን ነው ባብዬ የተረገዘው። አሁን የወላጆቼም ፊት እንደገና ተቋጠረ፣ “እንግዲህ ልጅ አይደለሽም! ኮስተር በይና ልጅሽን አሳድጊ!” አሉኝ፡፡ ባሌ ደግሞ በእጁ እንዳረገኝ ስላረጋገጠ ነው መሰል ባህሪው በጣም ከፋብኝም፡፡ አማራጭ ግን አልነበረኝም፡፡ ዘጠኝ ወሩን ከብዙ ስቃይ ጋር አሳልፌ ለመውለድ ወደ እናቴ ቤት ሄድኩ፡፡ ስቃዩም ልጅነቴም ተዳምረው ምጥን ብቻ ሳይሆን ሞትን አሳይተው መለሱኝ፡፡ እራሴም ልጅ እስሆንኩ ለልጁ ደንታ ባይኖረኝም፡፡ የፈጣሪ ፈቃድ ግን ሁለታችንም ከሞት አተረፈን፡፡ እናትነት ልዩ ሃይል አለው፡፡ ቁልቁልጭ እያለ ሳየው የልጅ አምሮዬ ሃላፊነትን ለመቀበል ተዘጋጀ፡፡ ቢሆንም ከዚህ በኋላ ከአባቱ ጋር እንደማልቀመጥ ቆርጬ ነበር፡፡
ልጄን ክርስትና አስነስቼ ከአራስ ቤት ከወጣሁ በኋላ ባለቤቴ ካልወሰድኩ ብሎ ይመላለስ ጀመር፡፡ አሁን እናትና አባቴ እንደድሮው ገርፈውና ተቆጥተው ሊልኩኝ አልሞከሩም፡፡ ምክንያቱም ከሞት የከፋ ውሳኔዬን ቀድሜ አስረድቻቸው ነበርና “ከእንግዲህ አይሆንም!” ሲሉ ሸኙት። ያን እለት ቢበሳጭም እኔን እንደሚያጠፋኝ ነበር የዛተው፡፡ አባቴ በህይወት እያለ ይህን ማድረግ ግን ቀላል አልሆነለትም። በውድ እንጅ በግድ ሊወስደኝ እንደማይችልም ደጋግሞ አረጋገጠ፡፡ “እልህ መርፌ ያስውጣል” ነው የሚባለው? አዎ እሱም አባቴን ለመግደል ከእልህ ይለፈ በቂ ምክንያት እንደሌለው ይሰማኛል፡፡ ምድር ያበቀለችው እኔን ብቻ አልነበረም፡፡ አባት ለልጁ ደህንነት መቆሙም በእኔ አባት አልተጀመረም፡፡ ብቻ መጥፎ ዕድል ሆነና የምወደውን አባቴን በእኔ ምክንያት በልጄ አባት አጣሁት፡፡ ሃዘኔም፣ መከራየም፣ ያን ቀን ጀመረ፡፡
የወንድሞቼ ቤት ከአባቴ ቤት ፈንጠር ፈንጠር ያለ ነበር። ተኩሱን ቢሰሙም የት እንደሆነ አውቀው የደረሱት ጠላት ተብየው ካመለጠ በኋላ ነው፡፡ ለነገሩ ወዲያው የገነፈለው ጎረቤትም ቢሆን አልደረሰበትም፡፡ የልቡን ሰርቶ ወዲያው ተሰወረ፡፡ በላይ በታች ብሎ ጠላቱን ማግኘትና መበቀል ያልቻለው ቤተ ዘመድ ደግሞ እኔንና ልጄን እንደሁለተኛ ጠላት አድርጎ ቆጠረን፡፡ ወንድሞቼ ትናንት ተንከባክበው ያሳደጉኝ እህታቸው መሆኔን እንኳን ማስታወስ አልፈለጉም። ልጄን ከጉያዬ ነጥቀው መግደል እኔን እንደጠላት ሚስትነቴ ማሰቃየት አማራቸው፡፡ ከጅምሩም ሁኔታው ስላላማረኝ የወላጆቼን ቤት ለቅቄ የወጣሁት ወዲያው ነበር፡፡ ወዴት መሄድ እንዳለብኝ እንኳን አላውቅም፡፡ ልጄን ይዤ ከአገር መጥፋት እንዳለብኝ ባስብም እንኳን አገር፣ የማውቀው ራቅ ያለ ቀበሌ አልነበረም፡፡ ቢሆንም የጭንቄን እግሬ እስኪደክመኝ ተጓዝኩ፡፡
*   *   *
“ያስደምማል አይደል? በጣም የሚገርም ጥበብ ነው! እንዴት ጎበዝ ሰዎች መሰሉሽ?” ቆሜ መቅረቴን ያው ሃላፊ ነበር ከሃሳቤ ያናጠበኝ፡፡ እንደመበርገግ ብዬ የሃፍረት ፈገግታ ፈገኩለትና፣ “አመሰግናለሁ! ይሄ የሁላችሁንም ብርቱ ጥረት ነው የሚያሳው!” አልኩት እውነትም ዝግጅቱ ሰራተኞቼ ሁሉ ምን ያህል ከልባቸው እንደተንቀሳቀሱበት የሚያሳይ ነው፡፡ እንደ አንቺ አየነት ብርቱ አለቃ ያለው ሰራተኛ ከዚህ ውጭ ሊሆን አይችልም፡፡ በእውነት በህይወቴ ከማደንቃቸው ብርቱ ሴቶች የመጀመሪያዋ ነሽ! ከወዲሁ እንኳን ለዚህ አበቃሽ እልሻለሁ፡፡ ሲል በአክብሮት ጎንበስ ብሎ ጨበጠኝ፡፡
“አመሰግናለሁ ግን ይሄ የሁላችንም ውጤት…” ለምን እንደሆን ባላውቀውም ንግግሬን ሳግ አቋረጠው፡፡ ከፊቱ ማልቀስ ግን አልፈለኩም እቃ እንደረሳ ሰው ተጣድፌ ወደ ቢሮዬ ገባሁ፡፡ ጸሃፊዬ ነገ የማደርገውን ንግግር ተይባ ጠረጴዛዬ ላይ አስቀምጣለች፡፡ ላነበው ግን አልቻልኩም። ለምን እንደሆን እንጃ ሆዴ ተረብሾብኛል፡፡ አልቅሽ የሚል ስሜት ነበር የተናነቀኝ፡፡ ለምን እንደማለቅስ ግን አልገባኝም፡፡ እስቲ በድሌ ቀን፤ ድሌን በማከብርበት ዋዜማ ምን ያስለቅሳል? ራሴን ጠየኩ እንጅ ስሜቴን መግታት አልቻልኩም ቢሮዬን ቆልፌ ስቅስቅ ብዬ አለቀስኩ፡፡ በዚህ ቀን ችግሮቼን ለምን እንደማስታወስ ባላውቅም ጭንቅላቴ የኋሊት እየራቀ እምቢ ብሎኛል፡፡ በዚህ ምቹ የቆዳ ወንበር ላይ ተቀምጨ አራስ ልጅ አዝየ የተንከራተትኩበት ተራራና ገደል ትውስታ እረፍት ነሳኝ፡፡


*   *   *
አባቴ ሲገደል ልጀ ገና ወር ከአስራ አምስት ቀኑ ነበር፡፡ ከዛ በኋላ የቆየሁት አስር ቀን እንኳ የሚሞላ አልነበረም፡፡ ልጄን እንደ አራስ ነብር ሁሉንም ለመንከስ ከሚሯሯጡት ወንድሞቼ ለማዳን ወገቤ ሳይጠና አዝየው ወጣሁ፡፡ የራቅኩት ግን ሁለት ቀበሌ ብቻ ነበር፡፡ ደከመኝ፣ መንገድ ላይ ተዝለፍልፌ ወደኩ። የአካባቢው ሰው ከእነልጄ ሰብስቦ ከአውሬ ያተረፈኝ፡፡ አብልተው አጠጥተው ቀና ስል የደረሰብኝን ጠየቁኝ፡፡
የገዳይ ልጅ በመገደሉ ላይ በተመሳሳይ እምነት ስላላቸው በደረሰብኝ መከራ አዘኑ እንጂ በሁኔታው አልተደነቁም፡፡ ሆኖም “ቢሆንስ እስኪያድግ የተብቃሉ እንጅ አራስ ልጅ ላይ ቃታ አይስቡ፣ ኧረ ይልቅ ዝም ብለሽ ተቀመጭና ልጅሽን አሳድጊ!”  ሲሉ ሌላ ስደት እንዳላስብ አበረታቱኝ፡፡
አንዳንድ ቤተዘመድ ለአራስ መጠየቂያ መቀነቴ ስር ከሸጎጠልኝ ብሮች በቀር ምንም ይዠ አልወጣሁም፡፡ ነገሩ ይዤስ ልውጣ ብል ማን ሊሰጠኝ፡፡ የጠላት ገንዘብ ባይወስዱት እንኳን ወፍ ይበላዋል እንጅ በምን መብቷ ሚስት ታዝበታለች። አይ! እርጉም ሥራ! ታዲያማ ሴት አይገደልም! ይሉናል፡፡ ሞት ከዚህ በላይ ምን አለ? በደከመ አካል ሃዘን፣ ረሃብ፣ ችግር፣ ስጋት… ተሸክሞ ከመኖር ሞት አስር እጅ አይሻልም? ዳሩ ለእኛ ግልግል ነገር አልተፈቀደም፡፡ እኔም እነዛን በሮች ቋጥሬ ለስቃይ ወጣሁ። ለጊዜው ያስጠጉኝ አንዲት በጠላ ንግድ የተሰማሩ ሴት ነበሩ፡፡ በነዛው ብሮች ገብስ ግዥና አብረን እንነግድ አሉኝ። ለጊዜው ደስታውን አልቻልኩትም ነበር፡፡ የተከፋሁት ትርፉ ስቃይ ብቻ መሆኑን ስረዳ ነው፡፡ የጠላ ስራ ስቃይ ነው፡፡ በራሴ ገዝቼ እኔው መከራ አይቼ የሰራሁትን ጠላ የሚያዙበት እሳቸው ነበሩ፡፡ ለፈለጉት ይሰጣሉ፣ ለፈለጉት ይሸጣሉ፡፡ እሳቸውም ቢሆን እንደ እንስራቸው ጠላ ለምደዋል፡፡ ትርፉ ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ የሆነብኝ ለእኔ ብቻ ነው፡፡ እንደልጅ ቆጠሩኝ መሰል ያለይሉኝታ አንገላቱኝ፡፡ በጣም ያቃጠለኝ ግን የልጄ መሰቃየት ነበር፡፡ ያን ሁሉ እየለፋሁ ለእሱ አንዲት ነገር የምገዛበት እንኳን አጣሁ፡፡ በልብስም፣ በምግብም፣ በአያያዝም ተጎዳ፡፡
ይሄኔ ነው የጠላውን ንግድ ለማቆም የተገደድኩት፡፡ ሴትዮዋ አይሆንም ቢሉም እምቢ ብዬ እህል ንግድ ጀመርኩ። ፈተናው ግን ቢብስ እንጅ የሚሻል አልነበረም፡፡ በጀርባዬ ልጅ በጭንቅላቴ ሃያና ሃያ አምስት ኪሎ እህል ይዠ ተራራ ገደል መጓዝ፡፡ ከንግዱ በላይ መጠጡን በትርፍነት ይዘውት የነበሩት ባለቤቷ ጠላውን ካቆምሽ ልጅሽን አልይዝም ስላሉኝ ከእኔ ጋር መንከራተት ግዴታው ሆነ፡፡ አንድ ቀን ከታችኛው ገባያ እገዛለሁ፡፡ ከቤቴ አድሬ በሌላው ቀን ወደ ላኛው ገበያ ወስጀ እሸጣለሁ፡፡ በቃ ከሚቀንሰው መግዛት፣ ተሸክሜ ወደሚጨምርበት ማጓጓዝ፡፡ በዚህ አይነት ለቀናት ተመላላስኩ፡፡ ስቃዩን ቃላት አይገልፁትም፡፡ ትርፉ ግን የተሻለ ሆነ፡፡ ልጀም ብርዱና ፀሃዩ ቢፈራረቅበትም ወተትና ጥብቆ አገኘ፡፡ በዚህ ሁኔታ እንዳለሁ ነበር የማስረክበው የእህል ነጋዴ አጠራቅመሽ ትወስጃለሽ እያለ ብሬን ማቆየት የጀመረው፡፡ ሁለት ሶስት አራት… ቢቸግረን እየተደበኩ ለሌላ ነጋዴ እየሸጥኩ የእለት ማገላበጫ ማግኘት ጀመርኩ፡፡ ቢሆንም እሱንም አልተውኩትም፡፡ እንዳለው ጠርቀም ብሎልኝ አህያ ለመግዛት አስቤአለሁ፡፡ አንድ ቀን ቁጭ በዬ ሳስበው እውነትም ለአህያ መግዣ የሚሆን አጠራቅሜአለሁ፡፡ እየተደሰትኩ ሄጀ አስረከብኩትና ለሚቀጥለው ቅዳሜ አዘጋጅቶ እንዲጠብቀኝ ስል ያሰብኩትንና ወደፊት ጨመር አድርጌ እንደማቀርብለት ነገርኩት፡፡ ለእለቱ በደስታ ተቀበለኝ፡፡በተባለው ቀን ግን ምንም ብር ሊሰጠን አልቻለም፡፡ ለካስ ለእሱም ስጋት ሆኘበት በፍርሃት ኖሯል የሚያስተናግደኝ፡፡
“ጠላታችን ለማሳደግ እሷን ትተባበራለህ ብለው እንዳስፈራሩትና ብሩን እንደቀሙት!” ነገረኝ፡፡ “አሁንም እየተከታተሉሽ ስለሆነ ልጁ ከፍ ብሎ ሳያውቁት ይዘሽው ብትጠፊ ይሻላል፡፡” ሲልም እያዘነ ምክር ቢጤ ለገሰኝ፡፡ ልጄን ከላዬ ላይ የነጠቀኝ ያህል ነበር የደነገጥኩት፡፡ ተሸክሜ የመጣሁት እህል ሳይገለበጥ መንገሩ ጠቀመኝ፡፡ ምን አልባትም ሆን ብሎ ያደረገውም ይመስለኛል፡፡ እንደደነገጥኩ እህሌን አንስቼ ሮጥኩ፡፡ ቢሆንም እንደሌባ ተሹለክልኬ ሸጥኩ እንጅ ወደ ቤቴ አልተመለስኩም፡፡
*   *   *
“እ እ.. እራት እዚህ ይቅረብልሽ እንዴ? መስቲ!” አዲሷ ልጅ ነበረች ጠያቂዋ፡፡ ሆቴሉ ስራ ከጀመረ ሰንበት ቢልም የተወሰኑት ገና የቅርብ ጊዜ ተቀጣሪዎች ስለሆኑና ባህሪዬን ስላላወቁ ይፈሩኛል፡፡ ስትገባ ባለመስማቴ እንደመበርገግ ብዬ መሸ እንዴ? ኧረ መኖሪያ ቤት እሄዳለሁ! እንደበረገኩ ተነሳሁ፡፡
“ስራ በዝቶብሽ ማደር የፈለግሽ መስሎን እንጅ እኮ መሽቷል” አለችን ለመውጣት ወደ በሩ እየተመለሰች፡፡ ግራ ገብቶኝ ሞባይሌን አንስቼ ሰዓት አየሁ፡፡ ገረመኝ የገባሁት ከመሸ ቢሆንም ይህን ያህል እቀመጣለሁ ብዬ አላሰብኩ፡፡ “ወይጉድ! ምን ነካኝ እባክሽ! በይ አንድ ሹፌር ጥሪልኝ አድርሰውኝ ይመለሱ፡፡ እውነትም በድርጊቴ እየተበሳጨሁ ቦርሳየን አንጠልጥዬ ወጣሁ፡፡ በቅርቡ ተጠናቆ የገባሁበት አዲሱ መኖሪያ ቤቴ ከከተማው ፈንጠር ስለሚል ከመሸ ብቻዬን እያሽከረከርኩ ለመሄድ እፈራለሁ፡፡ እሽ ብላ በፍጥነት ሄደች፡፡ ቢሮየን ቀልፌ እየተጣደፍኩ ሊፍት ጠራሁ፡፡ አልተያዘም፤ ፈጥኖ ሲደርስልኝ ገብቼ ቁጥሩን ነካሁ፡፡ ይዞኝ ቁልቁል ሸመጠጠ፡፡ ወደ መኪና ማቆሚያው እየተራመድኩ ግቢውን ቃኘሁ፡፡ እውነትም ሬስቶራንቱ አካባቢ ጭር ብሏል፡፡ ወዲያ የመኪና ማሞቅ ድምጽ ሰማሁ እሰይ! ሾፌር ተዘጋጅቶ እየጠበቀኝ ነው፡፡ ፈጠን ብዬ ገባሁና ቶሎ አድርሶኝ መመለስ እንዳለበት ነገርኩት፡፡ እሽታውን በአንገቱ ገልጾልኝ መኪናውን አስጓርቶ ከግቢ ወጣ፡፡ እሱም ፈራ መሰል እንደ በፍጥነት እያበረረ አድርሶኝ ተመለሰ። ቤቴ ስገባ ከዘበኛው በቀር ሁሉም ተኝተዋል፡፡ ለነገሩ እኔም የምግብ ፍላጎት አልነበረም፡፡ ቀጥታ ወደ መኝታ ቤቴ አመራሁ፡፡ ነገርን የኋሊት እያጠነጠነ ያለው ጭንቅላቴ ቢያርፍልኝ መተኛት ይኖርብኛል፡፡
*   *   *
የልጄን ነፍስ ለማዳን ነፍሴን ስቼ ያመለጥኩት ወደ ባህር ዳር ነበር፡፡ በእኔ ሸክም የመጣችው እህል ዋጋ ከትራንስፖርት ብዙ አልተረፈም፡፡ ቢሆንም ሁሉም ባለቆርቆሮ ሃብታም እንደሆነ ስላሰብኩ ከአንዱ ቤት የመጠጋት ሃሳብ ነበረኝ። ከተማ ሳይ የመጀመሪያዬ ነው፡፡ ከእኛ ገጠር ጋር ሲነፃጸር ብዙ ልዩነት እንዳለው ገብቶኛል፡፡ የነዋሪውን ልዩነት ያህል ግን አይሰፋም፡፡ እኔ ባገሬ መንገደኛ ሁሉ መሸብኝ ብሎ ሲጠለል ነው የማውቀው፡፡ እኔንም አቅፈው ደግፈው ያሳደሩኝ የማላውቃቸው የገጠር ሰዎች ነበሩ፡፡ እዚህ ግን እንዲያ የለም። የሰው ልጅ በየአስፋልቱ ተኝቶ ማየቱን ተላምደውታል፡፡ እኔም ያለኝ አማራጭ ከአንዱ ፌርማታ ስር ላስቲክ መከለል ነበር። ሁለታችንም እረሃብ ቢያዳክመንም የቀረችኝን ትንሽ ብር ለእለቱ በልቼ መጨረስ አልፈለኩም፡፡ ከሱቅ የተለያየ ነገር ገዝቼ በየመንገዱ እየተዘዋወርኩ መሸጥ ጀመርኩ፡፡ ለስቃይ ሆነ እንጅ ቆንጆ አድርጎ ነበር የፈጠረኝ፡፡ ገበያውን የሚያደራው ግን ካላቅሜ ልጅ አዝዬ መንከራተቴ ይመስለኛል፡፡ ብቻ ሁሉም እየጠሩ የሚፈልጉትንም የማይፈልጉትንም ይገዙኛል። እንዲህ እየዞርኩ በመነገድ ላይ እንዳለሁ ነው አንድ ሰው ለልጄም ለራሴም ደህንነት ባለው ሁኔታ እንድነግድ ቦታ በመስጠት የሚረዳኝ እንደሚፈልግልኝ ቃል የገባልኝ፡፡ ማንም ለማንም ይሰጣል ብዬ ስላልጠበኩ አላመንኩትም፡፡ ሰውየው ግን ቁምነገረኛ ነበር፡፡ በቀጠረኝ ቀን መጥቶ “እስቲ የአማራ ነጋዴ ሴቶች ማህበር የሚባል አለ ብለውኛል ልውሰድሽና የሚረዱሽ ካለ…”ሲናገር ለራሱም እርግጠኛ አይመስልም፡፡ ለዚህ ነው መሰል ሥራ እንዳያስፈታኝ እያሰብኩ በይሉኝታ የተከተልኩት። ግን ተሳስቼ ነበር፡፡ ያኑ እለት የሙያም የብድርም ድጋፍ እንደሚደርጉልኝ ቃል ገቡልኝ፡፡ መንገድ ላይ በሸጥኳትም ከልጄና ከእኔ ሆድ አትርፌ ትንሽ በቋጠርና ቤት መከራየት ችዬ ነበር፡፡ የተሰጠኝ የብድርና የሙያ ድጋፍ ግን ቤት ተከራይቼ የተለያዩ ነገሮችን እንድሰራ አበረታታኝ። እንጀራ ምግብ ባልትና ሁሉ አይቅረኝ አልኩ፡፡ ሃያ አራት ሰዓቱንም ሳልሸራርፍ ተጠቀምኩበት፡፡
በዚህ ላይ ተቀናቃኞቼ እንደሚሉኝ በመተት ባይሆንም ለገበያ ጥሩ እድል ያለኝ ይመስለኛል፡፡ የአማራ ነጋዴ ሴቶች ማህበርም በጥረቴ ተደሰተ መሰል ድጋፉን አበዛልኝ፡፡ በተለይ በሙያ አለመማሬ ጥፋት እንዳያመጣ አገዙኝ፡፡
“ቁልቁል ሲሄዱማ ሞልታል አዋራጅ እኛን የቸገረን የሚያዋጣው እንጅ!” ነበር ያለች ዘፋኟ መሬቱ ይቅለላትና አሁን ሳስበው ግን የተሳሳተች ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ወደላይ ለመውጣት ለፈለገም አዋጭ እንደማያጣ አይቻለሁ። ቁም ነገሩ እኛ የምንይዘው አቅጣጫ ነው፡፡ እኔም ለመውጣት የማደርገውን ጥረት ስላዬ ነበር የክልሉ ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋም እነሆ የመስሪያ ቦታ ያለኝ፡፡ እንኳን ዘንቦብሽ.. ነበር የሚባለው? እንኳን የቤት ኪራይ ሳልከፍል? ገቢዬ ሌላ ሆነ። የትናንቷ ጎዳና ተዳዳሪ ከሃያ በላይ ሰራተኛም ቀጠርኩ፡፡ ባልትናውም ሆቴሉም ጎን ለጎን አደጉ! በተለይ ልጀ ከተማይቱ አለኝ ከምትለው የግል ትምህርት ቤት መማር ጀመረ፡፡ በየጊዜው የሚሰጠኝ የሙያ ምክር ሳልማር ንቁ አድርጎኛል። ልጄም ነፍስ እያወቀ በሚችለው ሁሉ ይደግፈኝ ጀምሯል፡፡
ቢሆንም ይህን ባለ አምስት ኮኮብ ሆቴል ለመገንባት ቦታ ስጠይቅ ያመነኝ አልነበረም፡፡ “ደፋር ገጠሬ! በጭቃ የምትለቁጠው መሰላት እንዴ?” ያሉኝ እንደነበሩም በኋላ ሰምቻለሁ፡፡ እኔ ግን ጠንክሬ ገባፋሁበትና ጠየኩ፡፡ እነሱም እግዜር ይስጣቸው እንደሁሉም አክብረው የሚሟላውን አሟልቼ እንዳቀርብ በመጠየቅ ከእነሱም የሚገባውን አደረጉልኝ፡፡ እግዚአብሄር የሚጥሩትን ያግዛል፡፡ ይሄው ከግማሽ ሚሊየን ያነሰ ብድር ይዞ ሥራ ለመጀመርና ለምረቃ ተዘጋጅቷል፡፡ ከዚህ በላይ ትልቁ ድሌ ግን የባብዬ ምርቃት ነው። ከትናንት ወዲያ ከአዲስ አባባ ዩንቨርሲቲ ያውም በመዓረግ ተመርቋል፡፡ ጥህ ብቻም አይደል፣ የተመረቀበት ሕግ ይተገበር ዘንድ ታች ገጠር ድረስ ወርዶ እንደሚሰራ ቃል ገብቶልኛል፡፡ ይህን ሳስብ ነው እኔን የመሰሉ ብዙ ሴቶች እንዳይንገላቱ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጌ የሚሰማኝና የሚያረካኝ፡፡
*   *   *
ደንግጨ እንደተነሳሁ ነበር መለባባስ የጀመርኩት፡፡ ይህን ያህል አረፍዳለሁ የሚል ግምት አልነበረኝም፡፡ በሃሳብ ስባዝን አድሬ ለካስ እስኪረፍድ ተኝቻለሁ፡፡ ጉድ ነው! ያች ጅል ልጇን ድራለች! ያለው ሰውዬ አይነት? እስቲ አሁን በራሴ ጉዳይ ላይ ማርፈድ! እየተበሳጨሁ ፈጥኜ ለበስኩ። ደግነቱ ልብስ አዘጋጅቻለሁ፡፡ ለነገሩ ምን አዘጋጃለሁ አዲስ አበባ ለልጄ ምርቃትና ለዚሁ ጉዳይ የሚያምር ሃበሻ ቀሚስ ከነጫማውና ጌጣጌጡ ገዝቼ ነው የመጣሁት፡፡ እናም አሁን በፍጥነት ጠለቅ ጠለቅ አድርጌ ወጣሁ፡፡ እውነትም ስደርስ አዳራሹ በሰው ተሞልቶ ነበር፡፡ ደግነቱ ባብየ አልቀደመኝም። ከውስጥ የቆየሁ ለማስመሰል ከጣርኩ በኋላ አዳራሽ ገባሁ፡፡ ገና ከመቀመጤ እንዲመርቁ የተጠሩት ባለስልጣን ስለመጡ እንድቀበል የሆቴሉ ሃላፊ ጠጋ ብሎ ሹክ አለኝና ወጣሁ። ቀድሜ ያየሁት ግን ባብየን ነበር፡፡ በገዋን ደምቆ በጓደኞቹ ታጅቦ እየገባ ነው፡፡ ሳየው አልቅሽ አልቅሽ የሚለኝ መጣ፡፡ እንዴት አምሮበታል! አባቱ ባህሪ የለውም እንጅ ቆንጅዬ ነበር፡፡ እሱ ግን ከሁለታችንም አዋጥቶ ልዩ ስራ ሆኗል፡፡ ሌላውን ጥዬ ሄጀ እቅፍ አደረኩት፡፡ ባለስልጣኑ በሌሎች እንግዶቼና በአማራ ነጋዴ ሴቶች ማህበር አመራሮች ተከበው ለምረቃ የተዘጋጀውን ሪቫን መቁረጥ ጀምረዋል፡፡ ይህን ተከትሎ እልልታው ደመቀ፡፡ እኔ ግን ባብዬ ላይ እንደተጠመጠምኩ ነኝ፡፡ እሱን እንዳቀፍኩ እልል ለማለት ብሞክርም የደስታ እምባዬ ከለከለኝ፡፡ እምባ የደስታ መግለጫ ይሆናል ለካ? አነባሁት፡፡

Published in ህብረተሰብ

      ተከራይ ሆይ፤ የአዲስ አበባ አከራይ ሱዳናዊ እየመሰልነው መብራትና ውሃ ለእኛ ለተከራዮች መሸጥ ከጀመረ ከራርሟል፡፡ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ በሆነችው አዲስ አበባ፣ አንድ ሰው ቤት ሊከራይ ሲሄድ የመሬት ዋጋ የሚያህል ወርሃዊ ክፍያ ይጠየቃል። ታዲያ ተከራይ ከድንጋጤው ሲመለስ ሳልበላ ባድርስ በቤቴ ማን ያየኛል ይሁን ብሎ ቤቱን ሲከራይ ባለቤቶቹ ምንም እንዳይቀረው አድርገው ገንዘቡን አጥልለው ይወስዳሉ፡፡
አዲስ አበባ ላይ የተከራዩት ቤት ተጨማሪ የመብራትና የውሃ ክፍያ እንደሚያስጠይቅዎት እስካሁን ያውቃሉ ብዬ አገምታለሁ፡፡ እንደ ስለት ብር ከሌላ ገንዘብ ጋር እንዳይቀላቀል ይሆን እንዴ የቤት ኪራይ እንዲሁም የመብራትና የውሃ ክፍያን ለየብቻ የሚቀበሉት? ከዚህ በላይ የመክፈል አቅም የለኝም የሚሉ ከሆነ ቀላል ነው። አከራይዎ በመብራት፣ እርስዎ በሻማ መኖር ትጀምራላችሁ፡፡ ለነገሩ ይሄም ቢሆን ለአከራይ ሌላ የስራ እድል ይፈጥራል፡፡ ሻማ ከውጭ ይዞ መግባት አይቻልም ይሉና ለእርስዎ ብቻ ሻማ በእጥፍ ዋጋ መሸጥ ሊጀምሩ ይችላሉ፡፡ (በገዛ ቤታቸው ንግስናውን ማን ይወስድባቸዋል?)
አከራይ ሌላው ብቃቱ ምን መሰላችሁ? በፈለገው ሰዓት ከውጭ ሀገር ዘመድ ማፍራት መቻሉ ነው። የቤት ኪራይ ላይ ዳጎስ ያለ ጭማሪ ማድረግ ባማረው ጊዜ፣ ከውጭ ሀገር ከፈለገ ልጅ አሊያም ወንድም ያመጣል። የፈጠራ ማለት ነው፡፡ የሆነ ጊዜ ላይም “ወንድሜ coming soon” የሚል ፕሮፓጋንዳ ማሰራጨት ይጀምራል።  በተዘዋዋሪ የደረስዎ መረጃ ላይ እርምጃ ካልወሰዱ ወዲያው በቀጥታ ይደርስዎታል፡፡ ቤቱ ለወንድም ማረፊያ እንደሚፈለግ ይነገርዎታል፡፡
እርስዎ ከለቀቁ በኋላ እዚያች ቤት የሚገባው ግን የተባለው ወንድም አይደለም፡፡ ከእርስዎ የበለጠ መክፈል የሚችል፣ በደላላ የተገኘ ሌላ “ብራም” ተከራይ ነው፡፡ ዕድገት ሲመጣ ግላዊነት የሚያይል፣ማህበራዊነት እንደ ተከራይ ተክለ ሰውነት የሚቀጭጭ ይመስለኛል፡፡
ድሮ ድሮ አንድ ሰው በአጋጣሚ የሚያውቀውን ሰው ውይ ወንድሜ ቸገረው ብሎ ደባል ያደርገው ነበር አሉ፡፡ ዛሬ ዛሬ የቤት ኪራይ ሂሳብ ዝንፍ ያደረገ ተከራይ፣በባለቤቱና አጋሮቹ ተደብድቦ ሁሉ ሊባረር  ይችላል፡፡ ባለመብት ነዋ!
ምን እሱ ብቻ--- አብሮ መኖር ያመጣውን ትውውቅ የረሳ አከራይ፤ ተከራዬ እቃ ገዛ፣ ደሞዝ ጭማሪ አሊያም የሆነ ገንዘብ አገኘ ብሎ ሲያስብ ያለምንም ሃዘኔታ  ኪራይ ይጨምራል፡፡
“ዘመነ እኔ” ላይ፣ አንድ ግቢ ውስጥ አብረኸው የኖርከው ሁሉ ዘመድ ነው፡፡ ጎረቤት ደሞ-- ለችግርህ ደራሽ፣ ደስታህን ተካፋይ ብቻ አይደለም፡፡ ግዴታም ጭምር ያለበት ሁነኛ ሰው ማለት ነው። አሁን አንተ አንድ ግቢ አብረኸው ከምትኖረው አከራይህ ጋ የሚያገናኝህ “ለአምጪው እንዲከፈለው ህግ ያስገድዳል” የሚል የተፃፈበት የአከራይና የተከራይ ገንዘባዊ ግንኙነት ነው። በማንኛውም ሰአት አከራይህ የተሻለ ነገር ካገኘ በጨረታው አይገደድም።
ሌላው ለአከራዮች የሱዳን ዜጋ ሆነን እንደምንታያቸው የሚያረጋግጥልን ነገር---እንግዳ የሚባል እንዲመጣብህ አለመፈለጋቸው ነው። ዘመዶቻችን ሁሉ ከሀገር ውጪ ያሉ እየመሰላቸው ይሆን? ከሱዳን ኢትዮጵያ ትራንስፖርት ውድ ነው፤ አይመጡባቸውም--- ብለው ያስባሉ መሰል። ሱዳናዊ የኢተዮጵያን ቋንቋ እስኪለምድ፣ ጓደኛ አይዝም ብለውም ሳይደመድሙም አይቀሩም፡፡ እቤታቸው ብቻህን ኖረህ፣ ብቻህን እንድትወጣ ነው ህልማቸው፡፡
በተለይ የውሃ ጉዳይ ሃሳብ ውስጥ ስለሚከታቸው ቦንድ ገዝተን እየገደብን ያለነውን አባይን ጨምሮ የብዙ ወንዞች ባለቤት መሆናችንን ይዘነጉታል፡፡ ውሃውን ያለአግባብ በማፋሰስ ዕዳ ይከተናል በሚል -- ያውም በግልፅ በምትከፍለው ውሃ ላይ መብት አይሰጡህም። “በዘመነ እኔ”፣ ውሃ አስክሬን ማጠቢያ ነው፤ ለማንም አይነፈግም ይባላል። እንደኔ ነገረኛ የሆናችሁ ሰዎች፣እቺ አባባል አትጠፋችሁም። እስከ ወገብ አያያዙ ብዙ ጊዜ ስለተጠቀማችሁባት።
ተከራይ ሆነው ጆርዳና ሾ ከተመለከቱ ሆዳምና ጥሩ ምግብ የሚበሉ መስሎ ስለሚሰማቸው፣ እንዴት በለጠኝ በሚል ክራይ ሊጨምርብዎ አሊያም ሊያስወጣዎ ስለሚችል--- እባክዎ የቴሌቪዥንዎን ድምፅ ይቀንሱ፡፡
አቤቱ ላንተ ስልጣን የባቢሎንን ቋንቋ የለያየህ አምላክ ሆይ! እባክህን የተከራዮችን ስቃይ ተመልከትና፣ የአከራዮችን የገንዘብ ፍቅር በድማሚት ብትንትን አድርግልን። እኛ ፀሎታችንን እንደ ዓባይ ግድብ  አጠንክረን እናደርሳለን። አሜን! አሜን! አሜን!  

Published in ህብረተሰብ

“መንግስት የሌሎች አገራትን ያህል የነዳጅ ዋጋ የማይቀንሰው ለምንድነው?” ብለን ግን አንጠይቅም

     በያዝነው ሳምንት እና ከዚያም በፊት በኢዜአ የተሰራጩ ሁለት ሦስት ዜናዎችን ተመልከቱ። በአለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ቅናሽ እንደታየ የገለፁ የንግድ ሚኒስትር ዴኤታ፤ ከዚሁ ጋር የሸቀጣ ሸቀጦች ዋጋ ላይ ቅናሽ ግን አልታየም ሲሉ የአገሪቱን ነጋዴዎች እንደወቀሱ አትቷል ኢዜአ - ረቡዕ እለት ባሰራጨው ዜና። አዎ፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በአለም ገበያ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በግማሽ ያህል መቀነሱ እውነት ነው። የተጣራ ነዳጅ (ለምሳሌ የቤንዚን) ዋጋም እንዲሁ ቀንሷል - በ35 በመቶ ገደማ። በአገራችንስ ምን ያህል እንዲቀንስ ተደረገ? ወደ 15 በመቶ ገደማ ብቻ ነው የቀነሰው። ዋጋውን የሚተምነው ደግሞ የንግድ ሚኒስቴር ነው። በአገራችን የነዳጅ ዋጋ የሌሎች አገራትን ያህል ያልቀነሰው ለምን ይሆን? ኢዜአ ይህን ጥያቄ ለሚኒስትር ዴኤታው አላቀረበም። ነጋዴዎችን መወንጀል ነው ቀላሉ ነገር።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢኮኖሚክስ ረዳት ፕሮፌሰር ተሾመ አዱኛ፣ የአገሪቱ የንግድ አሰራር የገበያ  ህግንና ስርዓትን እንደማይከተል ጠቅሰው፤ ነጋዴዎች ግልፅነት በጎደለው አርቴፊሻል የዋጋ ትመና እንደሚሰሩ ተናግረዋል ይላል ኢዜአ። “ይህም በመሆኑ፣ በአለም አቀፍ ገበያ የነዳጅ ዋጋ ከ50 በመቶ በላይ በቀነሰበት ወቅት በኢትዮጵያ ሸቀጦች ላይ ግን ቅናሽ ሳይታይ ቀርቷል”በማለት እኚሁ ምሁር ማስረጃ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል። ለመሆኑ ኢኮኖሚስቱና ኢዜአ የት አገር ነው ያሉት? በአለም ገበያ ከታየው የነዳጅ ዋጋ ቅናሽ ጋር የሚመጣጠን የዋጋ ማስተካከያ ኢትዮጵያ ውስጥ ተግባራዊ እንዳይሆን የተደረገው በንግድ ሚኒስቴር የዋጋ ትመና እንጂ በነጋዴዎች ምርጫ አይደለም። በየወሩ የንግድ ሚኒስቴር የሚያወጣውን የዋጋ ተመን ራሱ ኢዜአ ይዘግባልኮ። ግን፤ ይህችን እውነታ ከማገናዘብ ይልቅ፤ የቢዝነስ ሰዎችን በጭፍን የመወንጀል ባህልን ጠብቆ ማቆየትና “ማስቀጠል” ይበልጥብናል መሰለኝ።
የንግድ ሚኒስትር ዴኤታውም እንዲሁ፤ የአገራችን የነዳጅ ዋጋ የሌሎች አገራትን ያህል እንዳይቀንስ የተደረገው በመስሪያ ቤታቸው የዋጋ ትመናና ውሳኔ መሆኑን ይዘነጉታል? ከአለም የነዳጅ ገበያ ጋር በአገራችን የሸቀጦች ዋጋ ያልቀነሰው ነጋዴዎች በሚከተሉት ብልሹ አሰራር ምክንያት እንደሆነ ነው ሚኒስትር ዴኤታው የሚናገሩት። ምን የሚባል ብልሹ አሰራር? ሚኒስትር ዴኤታው አንድ ሁለት እያሉ ይዘረዝራሉ። በንግዱ ማህበረሰብ ውስጥ ዋጋን በስምምነት የመወሰን አሰራር አለ ብለዋል። የተለያዩ ኩባንያዎችን በማዋሃድ ሞኖፖል የመፍጠር አሰራርም አለ ብለዋል።
እስቲ አስቡት። ኢትዮጵያ ውስጥ፣ የኩባንያ ባለአክሲዮኖች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጣሉ ኩባንያቸውን ለሁለት ለሶስት ሲሰነጥቁ እንጂ፤ ውህደት ሲፈጥሩ አይታችኋል? ወይስ ስለ ሌላ አገር ነው የሚናገሩት? የቢዝነስ ሰዎች የሸቀጦችን ዋጋ በስምምነት ሲወስኑስ የሚታዩትስ የት ነው? ኢትዮጵያ ውስጥ በተመሳሳይ ቢዝነስ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች፣ የሸቀጦችን ዋጋ በስምምነት ሊወስኑ ይቅርና፤ ሰላምታ ለመለዋወጥም ያህል የመቀራረብ ልምድ የላቸውም። የገበያ ውድድርን እንደጠላትነት ነው የሚቆጥሩት። ለነገሩ ሚኒስትር ዴኤታውም ይህንን እውነት አይክዱም። በንግድ ማህበረሰብ ውስጥ፣ ሁልጊዜ በተወዳዳሪነት ለመቀጠል በፅናትና በትጋት የመስራት ባህልን ከማሳደግ ይልቅ፤ አንዱ ተወዳዳሪ ሌላውን ለማጥፋት የመመኘት ባህል እንደሚታይ ገልፀዋል ዴኤታው።
እና እንዲህ አይነት ባህል ይታይባቸዋል የተባሉት ነጋዴዎች፤ በምን ተአምር ነው ከእለት ተእለት የሸቀጦችን ዋጋ በምክክር ለመወሰንና ከዚያም አልፈው ኩባንያዎቻቸውን ለማዋሃድ የሚስማሙት? ግን፤ እንዲህ አይነቶችን ጥያቄዎች እያነሳን ነገሩን መመርመር አንፈልግም - ብዙዎቻችን። በአጠቃላይ ለቢዝነስ ስራዎች አወንታዊ አመለካከት የለንማ። እንዲኖረንም አንፈልግማ። አንዳንዶቻችን ከእውቀት እጥረትና እጦት የተነሳ፤ የቢዝነስ ስራንና የቢዝነስ ሰዎችን በክፉ አይን እንመለከታለን። በእድሜ ገፋ ያሉት ብዙዎቹ ምሁራን፤ የደርግ አይነት የሶሻሊዝም አባዜ ተጠናውቷቸው “በዝባዥ ከበርቴዎችን” በመፈክር ማውገዝ ይናፍቃቸዋል። አንዳንዶቹ ወጣት ምሁራንም እንዲሁ፤ የቢዝነስ ስራንና የቢዝነስ ሰዎችን የሚያወግዝ የትምህርት ቅኝት ውስጥ ተነክረው ከወጡ በኋላ፤ ዞር ብለው ነገሩን ለመመርመር አይሞክሩም። ያንኑን ቅኝት ሲያስተጋቡ ይኖራሉ። በዚያ ላይ... ብዙዎቻችን በደፈናውና በጭፈን የታቀፍነው ነባሩ ፀረ-ቢዝነስ ቱባ ባህላችን ከጉያችን እንዲርቅ ፈቃደኞች አይደለንም። በማናቸውም ሰበብ ነጋዴዎችንና የቢዝነስ ሰዎችን በጭፍን ማውገዝና መወንጀል ለብዙዎቻችን ሱስ ሆኖብናል ማለት ይቻላል።
እንዲያ ባይሆን ኖሮማ፤ እውነታውን ለማየትና ለማገናዘብ ዳተኛ ባልሆንን ነበር። ከደርግ የሶሻሊዝም ስርዓት ወዲህ፤ መጠነኛ የነፃ ገበያ አሰራር በመፈጠሩ ብቻ፤ የቢዝነስና የንግድ ውድድር እንደተሻሻለ የበርካታ ኢኮኖሚስቶች ጥናት ያረጋግጣል። በየጊዜው የዋጋ ንረት የሚፈጠረውም፤ መንግስት አለቅጥ በሚያሳትመው የብር ኖት ምክንያት እንደሆነ የመንግስት መረጃዎች ያረጋግጣሉ። በ2000 ዓ.ም፣ ከዚያም እንደገና በ2003 ዓ.ም ጣራ የነካ የዋጋ ንረት የተፈጠረው፤ በሌላ ሰበብ ሳይሆን የብር ኖር በገፍ ስለታተመ ነው። የአገሪቱ ውስጥ የተሰራጨው የብር ኖት በግማሽ አመት ውስጥ በሃምሳ በመቶ ያህል ሲጨምር፤ ብር መርከሱና የዋጋ ንረት መከሰቱ ይገርማል እንዴ? ይሄው ነው በ2003 ዓም የተከሰተው። ራሱ መንግስት ለፓርላማ ያቀረበው ሪፖርት መሆኑንም ልብ በሉ።
እንዲያም ሆኖ፤ ሁሌም በነጋዴዎችና በቢዝነስ ሰዎች ላይ ነው የሚሳበበው። ለመሆኑ፤ ባለፉት ሶስት ዓመታት የዋጋ ንረቱ ረገብ ያለው፤ የነጋዴዎችና የቢዝነስ ሰዎች ባሕርይ ስለተለወጠ ይሆን? አይደለም። መንግስት የብር ህትመቱን ረገብ ስላደረገ ነው የዋጋ ንረት የተረጋጋው - ሙሉ ለሙሉ ባይጠፋም። እውነታው የዚህን ያህል ግልፅ ቢሆንም፤ ነጋዴዎችንና የቢዝነስ ሰዎችን በጭፍን የማውገዝ ሱሳችን እንዲቀርብን ስለማንፈልግ፤ እውነታውን አይተን እንዳላየን ማለፍን እንመርጣለን።
እስቲ ተመልከቱ። ከአመት በፊት የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በበርሜል፣ 110 ዶላር ገደማ ነበር። መቶ ሊትር ቤንዚን ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው ደግሞ በ100 ዶላር ገደማ እየተገዛ ወጪ ነበር። ያኔ የአንድ ሊትር የችርቻሮ ዋጋ በንግድ ሚኒስቴር ተመን 20 ብር ከ50 ሳንቲም ነበር የምንገዛው። ካለፈው ሰኔ በኋላ የነዳጅ ዋጋ መቀነስ ሲጀምር፣ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ወደ መቶ ዶላር፤ የመቶ ሊትር ቤንዚን ዋጋ ደግሞ ወደ 95 ዶላር ገደማ ወረደ - በነሐሴ ወር። ነገር ግን፤ የንግድ ሚኒስቴር በወቅቱ የችርቻሮ ዋጋ ለመቀነስ አልፈለገም። በአለም ገበያ ግን የነዳጅ ዋጋ በዚህ አላቆመም።
መስከረምና ጥቅምት ላይ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ወደ ዘጠና ብር፣ ከህዳር በኋላ ከሰባ ዶላር በታች ወርዶ ታህሳስ ላይ ነው 60 ቤት የገባው። የብሔራዊ ባንክ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ከጥቅምት እስከ ታህሳስ ወር ባለው ጊዜ ውስጥ፣ መቶ ሊትር ቤንዚን በአማካይ በ72 ዶላር ወጪ ነው ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ የነበረው። እንግዲህ አስቡት። የመቶ ሊትር ቤንዚን ዋጋ ከመቶ ዶላር ወደ 72 ዶላር ቀንሷል። ከታህሳስ ወዲህ ደግሞ ከ65 ዶላር በታች ሆኗል። በብር ሲመነዘር አንዱ ሊትር ከ13 ብር በታች ይሆናል ማለት ነው። የንግድ ሚኒስቴር ግን፤ የነዳጅ የችርቻሮ የአለም ገበያን በሚመጥን ሁኔታ እንዲቀንስ አላደረገም። 20 ብር ከ50 ሳንቲም የነበረውን የአንድ ሊትር ቤንዚን ዋጋ፤ ቢያንስ ቢያንስ ወደ 14 ብር ማውረድ ነበረበት። ግን አላደረገውም። 17 ብር ከ50 ነው ያደረገው።
ለምን? የተለያዩ አጓጉል ምክንያቶች ሲቀርቡ እንደነበር ታስታውሱ ይሆናል። በአለም ገበያ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ቢቀንስም የቤንዚን ዋጋ ያን ያህልም አልቀነሰም የሚል ሰበብ ቀርቦ ነበር። ይሄ ሃሰት ነው። የአለም ዋጋ ከመቀነሱ በፊት፣ ለበርካታ ወራት እየጨመረ ስለነበረ፣ ብዙም ለውጥ የለውም የሚል ማመካኛም ቀርቦ ነበር። ይሄም ሃሰት ነው። የነዳጅ ዋጋ ካለፈው ሰኔ ወር በፊት ለሁለት አመታት ያህል ብዙ ውጣውረድ አልነበረውም። እና እውነተኛው ምክንያት ምንድነው? ማለቴ የንግድ ሚኒስቴር የነዳጅ መሸጫ ዋጋ በአግባቡ ያልቀነሰበት ምክንያት ምንድነው? እስቲ በኢዜአ የተሰራጨ ሌላ ዜና ተመልከቱ።     
በአለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ በመቀነሱ መንግስት እንደተጠቀመ የገለፀው ኢዜአ፤ በስምንት ወራት ውስጥ የአንድ ቢሊዮን ዶላር ወጪ ለማዳን ተችሏል ሲል ዘግቧል። 20 ቢሊዮን ብር መሆኑ ነው። ነዳጅ ወደ አገር የሚገባበት ወጪ ከቀነሰ፤ ለምን የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በዚያው መጠን አልቀነሰም? መንግስት እንዳሰኘው ሊያተርፍብን ፈርልጎ ይሆን? የንግድ ሚኒስትር ዴኤታ በሰጡት ምላሽ፣ የነዳጅ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በተወሰደነ ደረጃ ብቻ እንደቀነሰ ጠቅሰው፤ ሌላው ትርፍ ግን እስካሁን የተከማቸ የውጭ እዳ ለመክፈል እየዋለ መሆኑን ገልፀዋል።

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ አዋቂና አንድ አላዋቂ በመንገድ ላይ እየተጓዙ ሳለ አንድ አውራዶሮ አጥር ላይ ሆኖ ሲጮህ ያያሉ፡፡
ይሄኔ አላዋቂው፤
“ይሄ አውራ ዶሮ እዚህ መሬት ላይ ሲጮህ‘ኮ እመንግስተ - ሰማይም ልክ ይሄንኑ የሚመስል አውራ ዶሮ በዚሁ ሰዓት ይጮሃል” ይላል፡፡
አዋቂው አዋቂ ነውና፤
“እኔ አይመስለኝም” ይላል፡፡
አላዋቂው፤
“ለምን? አስረዳኛ!”
አዋቂው፣
“አየህ እንደ ዶሮ ያለ ልክስክስና ኩሳም ነገር መንግስተ-ሰማይን ያህል ንፁህ ቦታ አይገባም” አለው፡፡
አላዋቂው አላዋቂ ነውና ለምን እሸነፋለሁ ባይ ነው፡፡
“አይ ዶሮው ሲጮህ አፉን ወደ መንግስተ-ሰማይ፣ ቂጡን ወደ ሲዖል አድርጎ ስለሆነ ምንም ችግር አይኖርም” ይላል፡፡
አዋቂው፤ አዋቂ ነውና አልለቀቀውም፡፡
“እኔ እንደሰማሁት ሲዖል እርጥቡን የሰው ስጋ እንኳን እንደጉድ ያነደዋል ነው የሚባለው፡፡ እንዲህ ያለውን የአውራ ዶሮ ላባማ እንዴት አድርጎ ይምረዋል?” ሲል ጠየቀ፡፡
ይሄኔ አላዋቂው፤ ቆጣና ፍጥጥ ብሎ፤
“ዎ!ዎ! እኔ ምን ቸገረኝ ያባቴ ዶሮ አይደለ ቢያንበገብገው?!” አለ፡፡
*       *       *
በየግል መድረኩ፤ በየመሸታ ቤቱ፣ በየሻይ ቤቱ፣ በየሬስቶራንቱ ወዘተ…  በዕውቀት መከራከር ከቀረ ውሎ አድሯል፡፡ የተማረ የማይከበርበት፣ ያልተማረ ዘራፍ ሲል የሚደመጥበት ሁኔታ እየበረከተ የመጣበት ዘመን ነው፡፡ በመናገርና አውቆ በመናገር መካከል ልዩነቱ ከመከነ ሰንብቷል! አገሩን፤ “እኔ ምን ቸገረኝ ያባቴ ዶሮ አደለች!” ብሎ በምንግዴ የሚያየው ዜጋ በሚያስገርም ሁኔታ እንደባክቴሪያ የሚራባበት አየር እየተፈጠረ ነው፡፡ አገርን መሰረት አድርጎ ፖለቲካን፣ ኢኮኖሚን አሊያም ባህልን ማየት የተነወረበት ጊዜ እየመጣ ይመስላል፡፡ አለማወቅና ስግብግብነት ሲቀናጁ ምን ዓይነት አደጋ ላይ እየጣሉን እንደሆነ ማየት ተስኖናል፡፡
ካፒታሊዝም፤ እናት - አይምሬ ነው! የገዛ ወላጁን ሳይበላ የማይተኛ ሥርዓት ነው፡፡ ሼክስፔር እንደሚለው፤
“ያባትክን አሟሟት ሰበብ፣ ለማወቅ ሲፈላ ደምህ
ወዳጁንም ጠላቱንም፣ አብሮ መጥረግ ነው በቀልህ??” ሊባል የሚችል ጣጣ ውስጥ እየገባን እንደሆነ ማስተዋል ደግ ነው
ካፒታሊዝም፤ “ለሰላምታም ለጭብጨባም ቫት የሚከፈልበት መሆኑን በአክብሮት እንገልፃለን” ሊያሰኘን የሚችል ምስጥም ዐይን - አውጣም ስርዓት መሆኑን አንዘንጋ፡፡ በአሁኑ ሰዓት ዕውቀት የሚያቀጭጭ ክፉ ባህል ጭበጨባ ነው! አደጋም ነው! ባመኑበትም ባላመኑበትም ማጨብጨብ፣ ባወቁትም ባላወቁትም ማጨብጨብ እርግማን ነው፡፡ ምክን (Reason) የማይገዛው ማህበረሰብ ለገደል ቅርብ ነው ይላሉ ጸሀፍት፡፡
“እባካችሁ ክቡር እምክቡራን
የተከበሩ፣ አቶ ወይም ወ/ሮ እገሌን ወደ መድረኩ ጋብዙልኝ” ይላል የመድረክ መሪው፡፡ ከዚያ ጭብጨባ ነው፡፡ ቸብ! ቸብ! ቸብ! ትንሽ ቆይቶ፤ “እባካችሁ የተከበሩ ክቡር እምክቡራን አቶ ወይም ወይዘሮ እገሌን ወደቦታቸው ሸኙልኝ!” አሁንም ቸብ!...ቸብ!...ቸብ!... ይቀጥላል፡፡ የጭብጨባ ባህል! የፓርቲ አባል ያጨበጭባል፡፡ የድርጅት አባል ያጨበጭባል፡፡ የጎሣ አባል ያጨበጭባል፡፡ ጓደኛና ቲፎዞ ያጨበጭባል፡፡ የተማረው ያጨበጭባል! ያልተማረው ያጨበጭባል! አዋቂው ያጨበጭባል! አላዋቂው ያጨበጭባል! ሃይማኖተኛው ያጨበጭባል! ሃይማኖት - አልባው ያጨበጭባል! የኪነ-ጥበቡ ሰው እያጨበጨበ ጭብጨባ ይቀላውጣል!... ከዚህ የጭብጨባ ባህል ማን ይገላግለን ይሆን? ለጭብጨባም የአየር ሰዓት የሚጠየቅበት ወቅት እየመጣ ነው፡፡
ከማቴሪያል ሙስና ወደ ህሊና ሙስና እየተሸጋገርን ይመስላል! የድንቁርና ሙስናና የዕውቅና ሙስና ምን ያህል እንደሚተጋገዙ የምናይበት ጊዜ ሩቅ አይደለም፡፡ ይሄ ሁሉ ሆኖ አውራ - ዶሮው መጮሁን ይቀጥላል፡፡ የውሻና ግመሎቹ ነገር (The dog barks but the caravan goes) አብቅቶ፤ ግመሎቹም ውሻዎቹም አውራ - ዶሮውን እያዳመጡ መከራከር የጀመሩበት ጊዜ ነው፡፡ አውራ ዶሮ የጮኸውን ያህል ክርክሩም ይጮሃል፡፡ ያገራችን ነገረ በተመለደና ባልተለወጠ ነገረ - ሥራ መጯጯህ መሆኑ ያሳዝናል!
ልማዳዊ አካሄዳችን አልለወጥ የሚለው ለውጥ ስለሌለ ይሆን? ሁሉ ነገር የልማድ፣ የወግ፣ የወረት (የfashion) ተገዢ የሆነ መምሰሉ ይገርማል፡፡ የእገሌ ራዕይ፣ ራዕይ፣ ራዕይ … እንደጀመርን … እንደጀመርን … (አንዴ ከገባንበት ስሜት ዓይነት ጭምር)… እንዳጋመስን … እንዳጋመስን … ስንጨርስስ? … እንደጨረስን… እንጨርሰዋለን … እንዳይሆን ያሰጋል፡፡ ከዘፈን ወደ መፈክር መሄድ፣ ከዘፈን ወደ ዘፈን ከመሄድ የተሻለ ነው ወይ? የሚለውን ለማረጋገጥ መሞከር ብልህነት ነው፡፡
የእኛው ፀሐፌ ተውኔት፣ ገጣሚ ፀጋዬ ገ/መድህን የሚለንን መስማት ደግ ነው፡-
“አንድ የፍየል ሙክት ቆዳ እያለፋ ስልቻ የሚያወጣና የሚያዜም ሰራተኛ ነበር፡፡ ደግሞ ጆሮ ደግፍ ይዞታል፡፡ እና ቆዳ ሲያለፋ በረገጠ ቁጥር ያመው ነበር፡፡ በዚያ ምክንያት ዘፈኑ ይበላሽበትና ወደ ለቅሶ ይለወጥበታል፡፡ ወደ ህመም ይለወጥበታል፡፡ ግን ህመሙን በዘፈኑ ማስታመም እንጂ ከእዚያ እቤት የሚሰማውን ቻቻታ መስማት አይፈልግም፡፡ እዚያማ የሙክቱ ሥጋ ይበላል፡፡ ሰዎች በደስታ ያሳልፋሉ፡፡ እሱ ግን እዚህ ቆዳ እያለፋ ይሰቃያል”
ያው ያንዱ ደስታ ላንዱ ዋይታ ነው፡፡ “ህመምን በዘፈን ማስታመም” አንዱ በሽታችን ነው፡፡ ፖለቲካችን የዚህ በሽታ ልክፍት እንዳለበት ልብ ካላልን አንድንም!
የሀገራችን ኢኮኖሚ፤ እሱን ተከትሎም የኑሮ ደረጃውን፤ ማመዛዘን ግራ አጋቢ ነው፡፡ በዚህ ፋሲካ ወይም በሌላ ማናቸውም ክብረ በዓል የሰውን አኗኗር ለማሰብ ብንሞክር፤ …ከዓመታት በፊት ዶሮ እንዴትና በምን ዋጋ ይበላ እንደነበር የሚተርክ ሰው ይገኛል፡፡ ዛሬ አይበላም፤ “አይ ኑሮ” ይላል፡፡ ሌላው ዶሮ አርዷል፡፡ በግም አርዷል፡፡ “የቅርጫውን ዋጋ አልቻልነውም‘ኮ፤ ይሄ ኑሮ ውድነት ተጫወተብን! አይ ኑሮ!” ይላል፡፡
የመጨረሻው ዶሮም አለው፡፡ በግም አርዷል፡፡ “በሬው ግን ከቄራ ይገዛ ወይስ ተነድቶ ከገጠር ይምጣ? ቀረጡ፣ ማስነጃው ሰማይ ወጣ እኮ!” “አይ ኑሮ!” እያለ ያማርራል፡፡ በዚህ ኢኮኖሚ ጥላ ሥር ፖለቲከኛው የራሱ ቋንቋ ነው ያለው፡፡ አሰብ ቢመለስ ኖሮ… አሥመራ ገብተን ቢሆን ኖሮ… በቂ የአየር ጊዜ ቢሰጠን ኖሮ… ሰብዓዊ መብት ቢከበር ኖሮ… ዲሞክራሲ ዕውነት ቢሆን ኖሮ… ኮንዶምኒየም በር የለው፣ መስኮት የለው፤ ውሃ የለው… የፕሬስ ችግር ቢፈታ ኖሮ…” አይ ኑሮ
አገራችን ከምትችለው በላይ ኑሮና ኗሪ ተሸክማ የምትጓዝ ናት፡፡ ይሄን ሁሉ ኑሮ፣ ድህነትና ሃሳዊ ጥጋብ መፍቻ ቁልፉ፣ የህዳሴው ግድብ ከነዙሪያ ገባ ዲፕሎማሲው ነው… ለማለት ለጤናማ ኢኮኖሚስትም ለጤናማ ሀገራዊ ፖለቲከኛም ያስቸግራል፡፡ አንድ ያላት ጥርስ በዘነዘና ትነቀስ አይሆንም፡፡ ዶሮ ብታልም ጥሬዋንም አይሠራም፡፡ ዘርፈ - ብዙና መረበ - ብዙ መፍትሔ እናገኝ ዘንድ ዘርፈ - ብዙ ልብ ይስጠን፡፡
በትንሣኤው ስለትንሣኤው እናስብ ዘንድ ልብና ልቦና ይስጠን!!” “ለሰው እንተርፋለን እንኳን ለራሳችን” የሚለው የዱሮ መፈክር፣ ትዝ ይለናል፡፡ ሁሌ እንግዳ ተቀባይ ነን እንደምንል ሁሉ፣ ሁሌ ለጋሥ ነን ማለትን እንፈልገዋለን፤ ቅንነታችን የተባረከ ይሁን!
በተጨባጭና ከልብ እንግዳ ተቀባይ፣ በተጨባጭና ከልብ ያለን የተረፈንና ለሌላ የምንለግስ ልንሆን ይገባል፡፡ በመብራቱም፣ በውሃውም፣ በቡናውም፣ በጤፉም፣ በበጉም በከብቱም የዚህ ዕውነታ ዕሙን ሊሆን ይገባል፡፡ አለበለዚያ “ሳይተርፋት አበድራ ሳትቀበል ሞተች” የሚለው ተረት ዕሙን ይሆናል!!   

Published in ርዕሰ አንቀፅ

“መንግስት የሌሎች አገራትን ያህል የነዳጅ ዋጋ የማይቀንሰው ለምንድነው?” ብለን ግን አንጠይቅም
     በያዝነው ሳምንት እና ከዚያም በፊት በኢዜአ የተሰራጩ ሁለት ሦስት ዜናዎችን ተመልከቱ። በአለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ቅናሽ እንደታየ የገለፁ የንግድ ሚኒስትር ዴኤታ፤ ከዚሁ ጋር የሸቀጣ ሸቀጦች ዋጋ ላይ ቅናሽ ግን አልታየም ሲሉ የአገሪቱን ነጋዴዎች እንደወቀሱ አትቷል ኢዜአ - ረቡዕ እለት ባሰራጨው ዜና። አዎ፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በአለም ገበያ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በግማሽ ያህል መቀነሱ እውነት ነው። የተጣራ ነዳጅ (ለምሳሌ የቤንዚን) ዋጋም እንዲሁ ቀንሷል - በ35 በመቶ ገደማ። በአገራችንስ ምን ያህል እንዲቀንስ ተደረገ? ወደ 15 በመቶ ገደማ ብቻ ነው የቀነሰው። ዋጋውን የሚተምነው ደግሞ የንግድ ሚኒስቴር ነው። በአገራችን የነዳጅ ዋጋ የሌሎች አገራትን ያህል ያልቀነሰው ለምን ይሆን? ኢዜአ ይህን ጥያቄ ለሚኒስትር ዴኤታው አላቀረበም። ነጋዴዎችን መወንጀል ነው ቀላሉ ነገር።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢኮኖሚክስ ረዳት ፕሮፌሰር ተሾመ አዱኛ፣ የአገሪቱ የንግድ አሰራር የገበያ  ህግንና ስርዓትን እንደማይከተል ጠቅሰው፤ ነጋዴዎች ግልፅነት በጎደለው አርቴፊሻል የዋጋ ትመና እንደሚሰሩ ተናግረዋል ይላል ኢዜአ። “ይህም በመሆኑ፣ በአለም አቀፍ ገበያ የነዳጅ ዋጋ ከ50 በመቶ በላይ በቀነሰበት ወቅት በኢትዮጵያ ሸቀጦች ላይ ግን ቅናሽ ሳይታይ ቀርቷል”በማለት እኚሁ ምሁር ማስረጃ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል። ለመሆኑ ኢኮኖሚስቱና ኢዜአ የት አገር ነው ያሉት? በአለም ገበያ ከታየው የነዳጅ ዋጋ ቅናሽ ጋር የሚመጣጠን የዋጋ ማስተካከያ ኢትዮጵያ ውስጥ ተግባራዊ እንዳይሆን የተደረገው በንግድ ሚኒስቴር የዋጋ ትመና እንጂ በነጋዴዎች ምርጫ አይደለም። በየወሩ የንግድ ሚኒስቴር የሚያወጣውን የዋጋ ተመን ራሱ ኢዜአ ይዘግባልኮ። ግን፤ ይህችን እውነታ ከማገናዘብ ይልቅ፤ የቢዝነስ ሰዎችን በጭፍን የመወንጀል ባህልን ጠብቆ ማቆየትና “ማስቀጠል” ይበልጥብናል መሰለኝ።
የንግድ ሚኒስትር ዴኤታውም እንዲሁ፤ የአገራችን የነዳጅ ዋጋ የሌሎች አገራትን ያህል እንዳይቀንስ የተደረገው በመስሪያ ቤታቸው የዋጋ ትመናና ውሳኔ መሆኑን ይዘነጉታል? ከአለም የነዳጅ ገበያ ጋር በአገራችን የሸቀጦች ዋጋ ያልቀነሰው ነጋዴዎች በሚከተሉት ብልሹ አሰራር ምክንያት እንደሆነ ነው ሚኒስትር ዴኤታው የሚናገሩት። ምን የሚባል ብልሹ አሰራር? ሚኒስትር ዴኤታው አንድ ሁለት እያሉ ይዘረዝራሉ። በንግዱ ማህበረሰብ ውስጥ ዋጋን በስምምነት የመወሰን አሰራር አለ ብለዋል። የተለያዩ ኩባንያዎችን በማዋሃድ ሞኖፖል የመፍጠር አሰራርም አለ ብለዋል።
እስቲ አስቡት። ኢትዮጵያ ውስጥ፣ የኩባንያ ባለአክሲዮኖች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጣሉ ኩባንያቸውን ለሁለት ለሶስት ሲሰነጥቁ እንጂ፤ ውህደት ሲፈጥሩ አይታችኋል? ወይስ ስለ ሌላ አገር ነው የሚናገሩት? የቢዝነስ ሰዎች የሸቀጦችን ዋጋ በስምምነት ሲወስኑስ የሚታዩትስ የት ነው? ኢትዮጵያ ውስጥ በተመሳሳይ ቢዝነስ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች፣ የሸቀጦችን ዋጋ በስምምነት ሊወስኑ ይቅርና፤ ሰላምታ ለመለዋወጥም ያህል የመቀራረብ ልምድ የላቸውም። የገበያ ውድድርን እንደጠላትነት ነው የሚቆጥሩት። ለነገሩ ሚኒስትር ዴኤታውም ይህንን እውነት አይክዱም። በንግድ ማህበረሰብ ውስጥ፣ ሁልጊዜ በተወዳዳሪነት ለመቀጠል በፅናትና በትጋት የመስራት ባህልን ከማሳደግ ይልቅ፤ አንዱ ተወዳዳሪ ሌላውን ለማጥፋት የመመኘት ባህል እንደሚታይ ገልፀዋል ዴኤታው።
እና እንዲህ አይነት ባህል ይታይባቸዋል የተባሉት ነጋዴዎች፤ በምን ተአምር ነው ከእለት ተእለት የሸቀጦችን ዋጋ በምክክር ለመወሰንና ከዚያም አልፈው ኩባንያዎቻቸውን ለማዋሃድ የሚስማሙት? ግን፤ እንዲህ አይነቶችን ጥያቄዎች እያነሳን ነገሩን መመርመር አንፈልግም - ብዙዎቻችን። በአጠቃላይ ለቢዝነስ ስራዎች አወንታዊ አመለካከት የለንማ። እንዲኖረንም አንፈልግማ። አንዳንዶቻችን ከእውቀት እጥረትና እጦት የተነሳ፤ የቢዝነስ ስራንና የቢዝነስ ሰዎችን በክፉ አይን እንመለከታለን። በእድሜ ገፋ ያሉት ብዙዎቹ ምሁራን፤ የደርግ አይነት የሶሻሊዝም አባዜ ተጠናውቷቸው “በዝባዥ ከበርቴዎችን” በመፈክር ማውገዝ ይናፍቃቸዋል። አንዳንዶቹ ወጣት ምሁራንም እንዲሁ፤ የቢዝነስ ስራንና የቢዝነስ ሰዎችን የሚያወግዝ የትምህርት ቅኝት ውስጥ ተነክረው ከወጡ በኋላ፤ ዞር ብለው ነገሩን ለመመርመር አይሞክሩም። ያንኑን ቅኝት ሲያስተጋቡ ይኖራሉ። በዚያ ላይ... ብዙዎቻችን በደፈናውና በጭፈን የታቀፍነው ነባሩ ፀረ-ቢዝነስ ቱባ ባህላችን ከጉያችን እንዲርቅ ፈቃደኞች አይደለንም። በማናቸውም ሰበብ ነጋዴዎችንና የቢዝነስ ሰዎችን በጭፍን ማውገዝና መወንጀል ለብዙዎቻችን ሱስ ሆኖብናል ማለት ይቻላል።
እንዲያ ባይሆን ኖሮማ፤ እውነታውን ለማየትና ለማገናዘብ ዳተኛ ባልሆንን ነበር። ከደርግ የሶሻሊዝም ስርዓት ወዲህ፤ መጠነኛ የነፃ ገበያ አሰራር በመፈጠሩ ብቻ፤ የቢዝነስና የንግድ ውድድር እንደተሻሻለ የበርካታ ኢኮኖሚስቶች ጥናት ያረጋግጣል። በየጊዜው የዋጋ ንረት የሚፈጠረውም፤ መንግስት አለቅጥ በሚያሳትመው የብር ኖት ምክንያት እንደሆነ የመንግስት መረጃዎች ያረጋግጣሉ። በ2000 ዓ.ም፣ ከዚያም እንደገና በ2003 ዓ.ም ጣራ የነካ የዋጋ ንረት የተፈጠረው፤ በሌላ ሰበብ ሳይሆን የብር ኖር በገፍ ስለታተመ ነው። የአገሪቱ ውስጥ የተሰራጨው የብር ኖት በግማሽ አመት ውስጥ በሃምሳ በመቶ ያህል ሲጨምር፤ ብር መርከሱና የዋጋ ንረት መከሰቱ ይገርማል እንዴ? ይሄው ነው በ2003 ዓም የተከሰተው። ራሱ መንግስት ለፓርላማ ያቀረበው ሪፖርት መሆኑንም ልብ በሉ።
እንዲያም ሆኖ፤ ሁሌም በነጋዴዎችና በቢዝነስ ሰዎች ላይ ነው የሚሳበበው። ለመሆኑ፤ ባለፉት ሶስት ዓመታት የዋጋ ንረቱ ረገብ ያለው፤ የነጋዴዎችና የቢዝነስ ሰዎች ባሕርይ ስለተለወጠ ይሆን? አይደለም። መንግስት የብር ህትመቱን ረገብ ስላደረገ ነው የዋጋ ንረት የተረጋጋው - ሙሉ ለሙሉ ባይጠፋም። እውነታው የዚህን ያህል ግልፅ ቢሆንም፤ ነጋዴዎችንና የቢዝነስ ሰዎችን በጭፍን የማውገዝ ሱሳችን እንዲቀርብን ስለማንፈልግ፤ እውነታውን አይተን እንዳላየን ማለፍን እንመርጣለን።
እስቲ ተመልከቱ። ከአመት በፊት የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በበርሜል፣ 110 ዶላር ገደማ ነበር። መቶ ሊትር ቤንዚን ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው ደግሞ በ100 ዶላር ገደማ እየተገዛ ወጪ ነበር። ያኔ የአንድ ሊትር የችርቻሮ ዋጋ በንግድ ሚኒስቴር ተመን 20 ብር ከ50 ሳንቲም ነበር የምንገዛው። ካለፈው ሰኔ በኋላ የነዳጅ ዋጋ መቀነስ ሲጀምር፣ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ወደ መቶ ዶላር፤ የመቶ ሊትር ቤንዚን ዋጋ ደግሞ ወደ 95 ዶላር ገደማ ወረደ - በነሐሴ ወር። ነገር ግን፤ የንግድ ሚኒስቴር በወቅቱ የችርቻሮ ዋጋ ለመቀነስ አልፈለገም። በአለም ገበያ ግን የነዳጅ ዋጋ በዚህ አላቆመም።
መስከረምና ጥቅምት ላይ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ወደ ዘጠና ብር፣ ከህዳር በኋላ ከሰባ ዶላር በታች ወርዶ ታህሳስ ላይ ነው 60 ቤት የገባው። የብሔራዊ ባንክ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ከጥቅምት እስከ ታህሳስ ወር ባለው ጊዜ ውስጥ፣ መቶ ሊትር ቤንዚን በአማካይ በ72 ዶላር ወጪ ነው ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ የነበረው። እንግዲህ አስቡት። የመቶ ሊትር ቤንዚን ዋጋ ከመቶ ዶላር ወደ 72 ዶላር ቀንሷል። ከታህሳስ ወዲህ ደግሞ ከ65 ዶላር በታች ሆኗል። በብር ሲመነዘር አንዱ ሊትር ከ13 ብር በታች ይሆናል ማለት ነው። የንግድ ሚኒስቴር ግን፤ የነዳጅ የችርቻሮ የአለም ገበያን በሚመጥን ሁኔታ እንዲቀንስ አላደረገም። 20 ብር ከ50 ሳንቲም የነበረውን የአንድ ሊትር ቤንዚን ዋጋ፤ ቢያንስ ቢያንስ ወደ 14 ብር ማውረድ ነበረበት። ግን አላደረገውም። 17 ብር ከ50 ነው ያደረገው።
ለምን? የተለያዩ አጓጉል ምክንያቶች ሲቀርቡ እንደነበር ታስታውሱ ይሆናል። በአለም ገበያ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ቢቀንስም የቤንዚን ዋጋ ያን ያህልም አልቀነሰም የሚል ሰበብ ቀርቦ ነበር። ይሄ ሃሰት ነው። የአለም ዋጋ ከመቀነሱ በፊት፣ ለበርካታ ወራት እየጨመረ ስለነበረ፣ ብዙም ለውጥ የለውም የሚል ማመካኛም ቀርቦ ነበር። ይሄም ሃሰት ነው። የነዳጅ ዋጋ ካለፈው ሰኔ ወር በፊት ለሁለት አመታት ያህል ብዙ ውጣውረድ አልነበረውም። እና እውነተኛው ምክንያት ምንድነው? ማለቴ የንግድ ሚኒስቴር የነዳጅ መሸጫ ዋጋ በአግባቡ ያልቀነሰበት ምክንያት ምንድነው? እስቲ በኢዜአ የተሰራጨ ሌላ ዜና ተመልከቱ።     
በአለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ በመቀነሱ መንግስት እንደተጠቀመ የገለፀው ኢዜአ፤ በስምንት ወራት ውስጥ የአንድ ቢሊዮን ዶላር ወጪ ለማዳን ተችሏል ሲል ዘግቧል። 20 ቢሊዮን ብር መሆኑ ነው። ነዳጅ ወደ አገር የሚገባበት ወጪ ከቀነሰ፤ ለምን የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በዚያው መጠን አልቀነሰም? መንግስት እንዳሰኘው ሊያተርፍብን ፈርልጎ ይሆን? የንግድ ሚኒስትር ዴኤታ በሰጡት ምላሽ፣ የነዳጅ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በተወሰደነ ደረጃ ብቻ እንደቀነሰ ጠቅሰው፤ ሌላው ትርፍ ግን እስካሁን የተከማቸ የውጭ እዳ ለመክፈል እየዋለ መሆኑን ገልፀዋል።


    በየሁለት ሣምንቱ እሁድ መርካቶ አንዋር መስጊድ አካባቢ 4 ሰአት ግድም የደረሰ ማንም ሰው አንድ የተለየ ክስተት መመልከቱ አይቀርም፡፡ ነገሩ አዲስ የሚሆንበት ለእንደኔ ዓይነቱ እንግዳ እንጂ የአካባቢው ነዋሪዎችማ ለምደውታል፡፡ ላለፉት ሦስት ዓመታት ሲካሄድ የቆየ አስደማሚም አስገራሚም ሰብዓዊ ተግባር ነው፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ በአካባቢው የሚታወቀው ብላቴናው አስመሮም ተፈራ፤ በመርካቶ ዙሪያ በየጎዳናው የወደቁ የአዕምሮ ህሙማንን እያነሳ ገላቸውን ያጥባቸዋል፡፡ ፀጉራቸውን ይላጫቸዋል፡፡ አዲስ ልብስ ያለብሳቸዋል፡፡ ምግብም ያበላቸዋል፡፡
የአዕምሮ ህሙማኑን የሚያጥብበት ሰወር ያለ ስፍራ ባለመኖሩ አውራጐዳና ላይ እርቃናቸውን ሲያጥባቸው ማየት የተለመደ ትዕይንት ነው፡፡
አስመሮምን ከልጅነቱ ጀምሮ እንደሚያውቁት  የሚናገሩት የ70 ዓመቱ የአካባቢው አዛውንት አቶ መሃመድ ጀማል፤ “ሰፈር ውስጥ ሲላላክልንና ሲያገለግለን ያደገ ልጅ ነው፤ አሁንም ሰዎች የሚፀየፏቸውን የአዕምሮ ህሙማን ለመንከባከብ የሚያደርገው ጥረት የታዛዥነቱና የቀናነቱ ነጸብራቅ ነው” ይላሉ፡፡ በልጅነቱ ከቤተሰቦቹ ተለይቶ በችግር ማደጉን እናውቃለን ያሉት አዛውንቱ፤ ያለፈበትን ህይወት አስታውሶ እነዚህን ምስኪኖች በሽታ አለባቸው፣ ተባያቸው ይተላለፍብኛል ሳይል ላለፉት ሦስት ዓመታት በቋሚነት ሲያጥባቸው፣ ሲያለብሳቸውና ሲመግባቸው ተመልክቻለሁ” ሲሉ እማኝነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ብላቴናው አስመሮም (ባሪያው) የተወለደው ከረዩ ሰፈር ቢሆንም ከቤተሰቦቹ ጋር በተፈጠረው አለመግባባት ገና የ8 ዓመት ህፃን ሳለ ነበር ወደ ጎዳና የወጣው፡፡ የአሜሪካን ግቢ ነዋሪዎች ባደረጉለት ድጋፍም በልጅነቱ በተለያዩ ስራዎች ላይ ለመሰማራት እንደቻለ ይናገራል። አስመሮም በየሁለት ሳምንቱ እሁድ ገላቸውን የሚያጥባቸው፣ ፀጉራቸውን የሚላጫቸውና ልብሳቸውን የሚቀይርላቸው እንዲሁም ምግብ የሚያበላቸው የአዕምሮ ህሙማን ቁጥር 25 ደርሰዋል፡፡ በዚህም የተነሳ እየተሳቀቅሁ በአደባባይ ርቃናቸውን ሳጥባቸው ተገድጄአለሁ ይላል፡፡ ይሄን ሰብዓዊ ተግባር ለመፈፀም ወጪው ከፍተኛ እንደሚሆን መገመት አያዳግትም፡፡ እሱ ደግሞ መኪና አጥቦ አዳሪ ነው፡፡
አስመሮም እንደሚለው፤ የታክሲ ሹፌሮች ባይኖሩ ኖሮ ይሄን በጐ ተግባር ለማከናወን አይችልም ነበር፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ባለፈው እሁድ በስፍራው ተገኝቶ ለህሙማኑ የሚደረገውን እንክብካቤ ከተመለከተ በኋላ ከወጣት አስመሮም ተፈራ ጋር በሰብዓዊ ተግባሩ ዙሪያ ተከታዩን አስገራሚና አስደማሚ ቃለምልልስ አድርጓል፡፡


“መልካም ሥራ ማለት የወንድምህን ስቃይ አይቶ አለማለፍ ነው”


መርካቶ አካባቢ ጐዳና ላይ የወደቁ የአዕምሮ ህሙማንን መንከባከብ የጀመርከው መቼ ነው?
የጀመርኩት በልጅነቴ ነው፡፡ ከ3 አመት ወዲህ ግን ቁጥራቸው እየበዛ በመምጣቱ  እንደምታየው በጐዳና ላይ ነው የማጥባቸው፡፡
ወደዚህ ሰብዓዊ ተግባር ለመግባት ያነሳሳህ ምንድነው?
በልጅነቴ እዚህ መርካቶ ጃሊያን ግቢ ስመጣ አፍራ የምትባል ልጅ ቁሽሽ ብዬ ታየኛለች፡፡ እቤታቸው ወስዳ ሰውነቴን አጥባኝ፣ ልብስ አለበሰችኝ፡፡ አንዳንዴ ቤተሰቦቿ “ከቤት አስወጪው” እያሉ ይቆጧት ነበር። እሷ ግን በድብቅ ሁሉ እያጠበች ምግብ ትሰጠኝ ነበር።
ያኔ እሷ ለእኔ ያደረገችልኝ በጐ ነገር፣ ያሳየችኝ ሰብዓዊነትና ርህራሄ ውስጤ ሰርፆ የገባ  ይመስለኛል፡፡ ቆሻሻዬን ሳትጠየፍ ነበር ከቤተሰቦቿ ተደብቃ የምታጥበኝ፡፡ ያኔ እኔ ገና 10 ዓመት እንኳ አልሞላምኝም ነበር፡፡ ዛሬ በተራዬ እኔም እነዚህን ሰዎች ስንከባከብ ደስታዬ ወደር የለውም፡፡ በጣም ነው የምደሰተው፡፡ የሚከፋኝ ይህን ማድረግ ካልቻልኩ ነው፡፡ አንድ ሰው የሚለብሰው ልብስ ካለው፣ እቤት የሚያስቀምጠውን ትርፍ ልብስ ለምን ለታረዘው ወንድሙ አያለብሰውም? አንዳንድ ሰው እኮ ከአምስት አመት በላይ ሳይለብሰው አይን አይኑን እያየ የሚያስቀምጠው ልብስ ቤቱ ይኖረዋል። እስቲ አስበው… የሰብአዊ ፍጡርን ዋጋ እንዴት ሰው ሠራሽ ከሆነው ጨርቅ እናሣንሰዋለን?! ተቀዶ አልቆ የሚጠፋውን ጨርቅ ለነፍሳችን መልካም ሰርተንበት፣ የታረዘውን አካል ብናለብስበት ምን አለ?!
እኔ አሁንም በዚህ አስተሳሰብ ስለተቃኘሁ ይሄን ከማድረግ ወደ ኋላ አልልም፡፡ ፈጣሪ ወገኖችህን በዚህ መልኩ አገልግል ብሎ ስላዘዘኝ፣ ጉድጓዴ እስኪማስ ድረስ ይሄን ከማድረግ ወደ ኋላ አልልም፡፡ እነዚህ ወገኖቻችን እኮ አዕምሯቸው ታመመ እንጂ እንደኛው ስጋ ለባሽ ናቸው፡፡ ይበርዳቸዋል፣ ይጠማቸዋል፣ ይታረዛሉ፡፡ እኛ ለአንድ ቀን ገላችንን ካልታጠብን አሳከከኝ እንል የለ እንዴ! እነሱ እኮ ስንት አመት ሙሉ ልብሳቸው በገላቸው ላይ ተጣብቆ ነው ያለው። እናም አፍንጫችንን ይዘን ከምንሸሻቸው ለምን አናፀዳቸውም? ይሄን ብናደርግ ምን ይጐድልብናል? መልካም ስራ ማለት እኮ የስጋ ለባሽ ወንድምህን ስቃይ አይቶ አለማለፍ ነው፡፡
አየህ የአዕምሮ  ህሙማን  እራበኝ ብለው መናገር አይችሉም፡፡ ወይ ፈዘው አይን አይንህን ያዩሃል እንጂ እርቦኛል አይሉህም፡፡ እንዲህ ዓይነት ሰዎች በየጐዳናው እያሉ፣ የተራረፈንን እንጀራ ገንዳ ውስጥ የምንደፋ ከሆነ፣ የኛ ሰብአዊነት ምኑ ጋ ነው። በዚህ አጋጣሚ እንጀራ ገንዳ ውስጥ የሚደፉ ሰዎች፣  ለአንዱ የተራበ ወገናቸው ቢሠጡት፣ እነሱ በመስጠታቸው ደስታን ሲያገኙ፣ ያ ሰው ደግሞ በልቶ በማደሩ ህይወቱን ያተርፋል፡፡
ገላ ማጠቡን እንዴትና በምን አጋጣሚ ጀመርከው?
አንድ ጊዜ አንዲት ልጅ እዚሁ (አሜሪካን ግቢ) አካባቢ የወር አበባዋ ፈሶ መሬት ላይ ወድቃ ነበር። የሚያያት ሰው ሁሉ ከንፈሩን እየመጠጠ፣ አንድና ሁለት ብር እየሰጣት ሲያልፍ አያለሁ፡፡ ምን ማለት ነው ብር መስጠት ብዬ ተገረምኩ፡፡ እቺን ልጅ አንስቼ ባጥባት እጄ አይቆረጥ አልኩና አንስቼ አጠብኳት፤ የእነ ካሊድ እናት (የአካባቢው ነዋሪ ናቸው) የውስጥ ሱሪዎችንና አልባሳትን ሰጠችኝ፡፡ በቃ በዚያች ልጅ ሰበብ ውስጤ የፈቀደውን ተግባር ማከናወን ማድረግ ጀመርኩ፡፡
ከታጠቡ በኋላ ምግብም ታበላቸዋለህ፡፡ ምግቡን ከየት ነው የምታገኘው?
ምግቡን ቀድሜ ነው የማዘው፡፡ አንድ ምግብ 15 ብር ነው፡፡ ገላቸውን ስናጥባቸው የሚያዩን  ሰዎች በሚሰጡን እርዳታ ነው ምግቡን የምገዛው። ሌሊት ተነስተው ውሃ ለሚቀዱልኝና ለሚያግዙኝ ሰዎችም እከፍላቸዋለሁ፡፡ ገላቸውን ከታጠቡ በኋላ ልብሳቸውም በአዲስ ስለሚቀየርላቸው ወጪ አለው። ለ25 ህሙማን በአንድ እሁድ… ለምግብ፣ ለውሃ፣ ለልብስ፣ ለሣሙና፣ ለፂምና ፀጉር መላጫ እስከ 3500 ብር የፈጃል፡፡ ይሄ ወጪ በአብዛኛው የሚሸነፈው በመንገድ ላይ ሲያልፉ የምንሰራው አስደስቷቸው ገንዘብ በሚለግሱን ሰዎች ነው፡፡
አብዛኛውን ድጋፍ የምታገኘው ከማን ነው?
እውነቱን ልንገርህ… የሁልጊዜም ተባባሪዎቻችን የታክሲ ሹፌሮች ናቸው፤ እነሱ ካለቻቸው ላይ ሣይሰጡን አያልፉም፡፡ ተሳፋሪያቸውንም ያስተባብራሉ፡፡ እኔ በአብዛኛው ልብስ ከነጋዴዎች ስገዛም ሆነ ምግብ ሣዝ እጄ ላይ ምንም ሣይኖረኝ፣ ከህብረተሰቡ የሚሰበሰበውን ተማምኜ ነው፡፡ አንዳንዴም ካልተሟላ ራሴ እንደምንም ብዬ እዳዬን እከፍላለሁ፡፡ የታክሲ ሹፌሮች ባይኖሩ እነዚህን ሠዎች በዚህ መልኩ ማልበስም ሆነ መመገብ አልችልም  ነበር፡፡ የእነሱ ድጋፍ ወደር የለሽ ነው፡፡
በአካባቢው ላይ ያሉ ሰዎችም ከፍተኛ ድጋፍ ያደርጉልኛል፡፡ የእነ ካሊድ እናት ነኢማ፣ አደሬ፣ እነ አብዲ ባሪያው… ምን ልበልህ… በቃ የጃሊያ ሠፈር ህዝብ በጣም ተባባሪዬና ደጋፊዬ ነው፡፡ እኔ ውልደቴ ከረዩ ሠፈር ቢሆንም ያሳደገኝ የጃሊያ ህዝብ፣ ድጋፉ ባስፈለገኝ ጊዜ ሁሉ ፊቱን አዙሮብኝ አያውቅም፡፡
የአዕምሮ ህሙማን እንደመሆናቸው መጠን ለማጠብ ስትይዟቸው አያስቸግሩም?
እሱማ ያስቸግራሉ፡፡ ያው ታግለን ለሦስት ለአራት ሆነን ተሸክመን እናመጣቸዋለን፡፡ አንዴ ምን ሆነ መሠለህ? አሻሮ ይባላል፣ የአዕምሮ ህመምተኛ ነው፡፡ በጣም ጉልበተኛ ነው፡፡ እኔ እግሩ ስር ገብቼ ሁለት እግሩን ግጥም አድርጌ ይዤው ለአራት ተሸክመነው መጣን፡፡ አምጥተን ልክ ሁለት ባልዲ ውሃ ስናፈስበት፤ “ኡፍ…” አለና  ፀጥ ብሎ ተቀመጠ፡፡ ብታምንም ባታምንም ውሃ ሰውን ያረጋጋል፤ የተለየ መንፈስ ያመጣል፡፡ ከዚያ በኋላ ራሱ ሣሙና እየመታ መታጠብ ጀመረ፡፡ ፀጉሩን ተላጨ፡፡ በመጨረሻ በተረጋጋ ስሜት፤ “እግዚአብሔር ይስጥልኝ” ብሎ ሄደ። በተደጋጋሚም ቀኑን ቆጥሮ ራሱ መጥቶ ይታጠብ ነበር፡፡ አሁን ግን ወዴት እንደሄደ አላውቅም፤ ጠፍቷል፡፡
ህመማቸው የተሻላቸውና ስራ የጀመሩት በአብዛኛው ራሣቸው መጥተው ይታጠባሉ፡፡ ያልተሻላቸውን በየሁለት ሳምንቱ እሁድ ጠዋት እየዞርን ተሸክመንም ቢሆን አምጥተን፣ አጥበናቸው ልብስ ቀይረንላቸው፣ ምግብ አብልተናቸው እንሸኛቸዋለን፡፡ ታዲያ እንዲያ ሲወራጩ የነበሩት ከታጠቡ በኋላ የተረጋጉ ሰው ሆነው ይሄዳሉ፡፡
አንተ በምን ሥራ ነው የምትተዳደረው?
በአነስተኛ ደላላነት እና መኪና በማጠብ (ላቢያጆ) ስራ ነው፡፡ ሌላ ነገር የለኝም፤ የምኖረውም በዚህች የቆርቆሮ ዳስ ውስጥ ነው (2x1 የሆነች የመንገድ ላይ የቆርቆሮ የጥበቃ ቤት ናት፡፡) እነሱም እዚሁ መጥተው አብረውኝ እየተጫወቱ ነው የሚያድሩት፡፡ ምን አለፋህ… ህይወቴ በሙሉ ከነሱ ጋር የተሳሰረ ነው፤ ልለያቸው ብልም አልችልም፡፡   
ከመንግሥትም ሆነ ከሌሎች ድርጅቶች የተደረገልህ ድጋፍ አለ?
እስካሁን ምንም የተደረገልኝ ድጋፍ የለም፡፡ እኔ ዛሬ እነዚህን ሰዎች የማጥበው ህዝብ እያየ ጎዳና ላይ ነው፡፡ ቦታ ቢኖረኝ ግን ክብራቸውን በጠበቀ መልኩ እንዲታጠቡ ማድረግ እችል ነበር፡፡  ብዙ ጊዜ ሴቶች፤ “ኧረ እባክህ እኛንም እጠበን” ይሉኛል፡፡ እንዴት አድርጌ ነው የማጥባቸው? ሴት ልጅን አደባባይ ላይ ማጠብ ነውር ነው፡፡ እዚህ አካባቢ አንዲት ከመሬት መነሳት የማይችሉ አሮጊት ሴትዮ አሉ፤ ባየኋቸው ቁጥር አዝናለሁ፡፡ እሳቸውም፤ “ኧረ እባክህ ልብሱ በላዬ ላይ እየተጣበቀ ነው” ይሉኛል (በላብ ማለት ነው) ግን ምን ማድረግ እችላለሁ? አስቸጋሪ ነው፡፡ በጣም የቸገረኝ ሴቶቹን የማጠቢያ ቦታ ነው፡፡ ወንዶቹንም ቢሆን ቦታ በማጣት መንገድ ላይ ማጠቤ ያሳቅቀኛል፡፡ ቦታ ቢኖረኝ ግን አብረውኝ ሁሉ እየኖሩ ብንከባከባቸው ደስ ይለኝ ነበር፡፡ በተሻለ መንገድ የበለጠ ብንከባከባቸው ነፍሴ ትረካለች፡፡
ሌሎች የምትንከባከባቸው አቅመ ደካሞች እንዳሉም ሰምተናል…
አንተ መንገድ ላይ ያሉትን ትላለህ… ፀሃይና ጨለማን ለይተው የማያውቁ በየቤቱ አሉ፡፡ ጎረቤት ዞር ብሎ የማያያቸው፣ ሰው የራባቸው ስንቶች አሉ። እሁድ ከሰዓት ሁሌ የምጎበኛቸው ሰዎች አሉ፤ ስሄድ እንዴት ደስ እንደሚላቸው! 10 ልጆቻቸው ሞተውባቸው በድንጋጤ ታመው አልጋ ላይ የዋሉ እናት አሉ፡፡ ቤታቸው ሰው አይገባም፡፡ እሳቸውም ከቤታቸው መውጣት አይችሉም፡፡ አንድ ቀን እህቴ ስለሴትየዋ ነግራኝ ቤታቸውን አሳየችኝ፡፡ ስገባ ቤቱ በጣም ይሸታል፡፡ ከጓደኞቼ ጋር ሆነን ቤቱን አፀዳን፣ እሳቸውንም አጠብናቸውና፤ “ማዘር ምን እንዲደረግልዎት ይፈልጋሉ?” አልኳቸው፡፡ “እኔ ምግብም ገንዘብም አልፈልግም፤ የራበኝ ሰው ነው፤ የምፈልገው ሰው ብቻ ነው” አሉኝ፡፡ አሁን በየጊዜው እየሄድን እንጠይቃቸዋለን፡፡ በዚህ አጋጣሚ አንዳንዴ ጎረቤቶቻችንን መጐብኘት መልካም ነው እላለሁ፡፡
እግዚአብሔር ይመስገን… እኔ የተሻላቸውንና የመስራት አቅሙ ያላቸውን በደላላነቴ የተዋወቅኋቸውን ሰዎች እያስቸገርኩ ስራ እንዲያገኙም አደርጋለሁ፡፡ አሁን ጤነኛ ሆነው በሞራል ስራ መስራት የጀመሩ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ሰው ሰርቶ አምስት ብር ሲያገኝና ለምኖ ሲያገኝ አንድ አይደለም፡፡ ሰርቶ ያገኘው ያስደስተዋል፣ ይቆጥበዋል፤ በልመና ያገኘው አያስደስተውም፤ ምናልባት የእለት ጉርሱን ሊሸፍንለት ይችላል፤ ነገር ግን ዘላቂ አለመሆኑን ሲያውቀው ደስታ ይርቀዋል፡፡
ከወደቁበት ጐዳና ተነስተው የተሻለ ህይወት የሚመሩ ሰዎች አሉ?
አዎ! አንድ የጎንደር ልጅ ነበር፡፡ ስሙን መጥቀስ አልፈልግም፡፡ ከብዙ ዓመታት በፊት አባቱ ከመርካቶ እቃ አስጭነህ ና ብለው ገንዘብ አሲዘው ይልኩታል። እዚህ ሲመጣ ብሩን ይዘረፋል፡፡ የዛሬ 4 ዓመት ገደማ ተክለሃይማኖት አካባቢ ጸጉሩ እላዩ ላይ ተድበልብሎ፣ ጎዳና ላይ ወድቆ እናየዋለን፡፡ “ለምን ይሄን ልጅ አናጥበውም” እንልና በግድ ይዘን እየጮኸ እናጥበዋለን።
ሲታጠብ የእግዚአብሔርን ስም እየጠራ ያመሰግን ነበር፤ ፀጉሩን ላጨነው፤ አዲስ ልብስ አለበስነው፤ ጥሩ ምግብ አበላነው፡፡ ወዲያው “እባካችሁ የጎንደር መሳፈሪያ ስጡኝ፤ ሃገሬ ልግባ” አለን፡፡ እኛም ከህዝቡ (ህዝቡ ስልህ እዚያው የነበሩ ምስኪኖች ጭምር አዋጥተውለታል) አሰባስበን ላክነው፡፡ ጎንደር ሲሄድ እናትና አባቱ ሞተው፣ አንድ እህቱ ብቻ ቀርታለች። ያ ልጅ ከ3 ዓመት በኋላ ባለፈው መጣና “እዚህ አካባቢ አንድ ጥቁር ልጅ ፈልጌ ነው” ይላል፤ እኔን መሆኑ ነው፡፡ “አስመሮም ሰላም ነህ?” አለኝና አለቀሰ፤ እህቱም አብራው ነበረች፤ አለቀሰች፡፡ ሻይ እየጠጣን “አላወከኝም?” አለኝ፤ “አላወኩህምም” አልኩት፡፡ ጭንቅላቱ ላይ የነበረውን ኮፊያ አውልቆ፣ ሳጥበው የማውቀውን ጠባሳ ሲሳየኝ በጣም ነበር የደነቀኝ፡፡ ከዚያ በኋላ የተለያዩ ድጋፎችን አድርጎልኝ፤ እሱም በተራው ስናጥብ አግዞን ሄደ፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ከእህቱም ከእሱም ጋር በስልክ እንገናኛለን፡፡
ሌላ የምታስታውሰው ተመሳሳይ ገጠመኝ አለህ?
አዎ! ልጁ የደህና ቤተሰብ ልጅ ነው፡፡ እዚሁ ከወደቀበት አንስተን ልብሱን ስንቀይርለት፤ “ለገሃር አካባቢ ወንድሜ አለ፤ ሱቅ ከፍቶ ይሰራል አገናኙኝ” አለ፡፡ ይዤው ሄጄ የተባለው ሱቅ ቀድሜ ገባሁና፤ “እገሌ የሚባል ወንድም አለህ?” አልኩት ባለሱቁን፡፡ “አዎ፤ ከጠፋ ብዙ ጊዜ ሆኖታል” አለኝ፡፡ “ይኸው” ብዬ ሳገናኘው፤ እምባውን መቆጣጠር አልቻለም፡፡ እንዲህ አይነት ብዙ ገጠመኞች አሉ፡፡ ሰው ከወደቀበት ተነስቶ ንፁህ ሲሆን ተስፋው ይለመልማል፣ ስነልቦናው ይታደሳል፡፡ ህክምና የሚያስፈልጋቸው ካሉም፣ 6 ኪሎ አካባቢ አንዲት ፈረንጅ ሃኪም አለች፤ እሷ ጋ እወስዳቸውና በነፃ ታክምልኛለች፡፡

     በቅርቡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዋጋ መቀነሱን ተከትሎ በትራንስፖርት አገልግሎት ታሪፍ ላይ ቅናሽ ቢደረግም በፋሲካ ገበያ የሸቀጦች ዋጋ ጭማሪ ማሳየቱን ሸማቾችና ነጋዴዎች ተናገሩ፡፡
የአዲስ አድማስ ሪፖርተሮች በአዲስ አበባ በሚገኙ የተለያዩ የገበያ ስፍራዎች ተዘዋውረው ባደረጉት ቅኝት፤ ሠንጋ በሬዎች ከ8ሺህ እስከ 17 ሺህ ብር ሲሸጡ፣ የፍየል ዋጋ ከዓምናው የፋሲካ በአል የ300 ብር ጭማሪ በማሳየት ከ2ሺ 4500 ብር እየተሸጠ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የበግ ዋጋ በሾላ ገበያ ትንሹ 1500 ብር፣ መካከለኛው እስከ 1800ብር እንዲሁም ትልቁ  እስከ 3500 ብር ሲሸጥ፣ በሣሪስና ጐተራ አካባቢ ትንሹ እስከ 1800 ብር፣ መካከለኛው 2500 ብር፣ ትላልቅ የሚባሉት ደግሞ እስከ 4000 ብር የሚገኙ ሲሆን መሲና የሰቡ ሴት በጐች ከ2200 እስከ 3ሺህ ብር እየተሸጡ ነው፡፡
በሾላ ገበያ የሚገኘው የከብቶች መሸጫ ቦታ በመንግስት በመውሰዱ፣ ሰሞኑን ነጋዴዎች ከደንብ አስከባሪዎች ጋር እየተሳደዱ በየመንገዱ ሲሸጡ የነበረ ሲሆን ከከተማው ርቆ በሚገኘው የካራ ገበያ እንዲጠቀሙ ማሳሰቢያ እንደተሰጣቸውም ተናግረዋል፡፡ የካራ የገበያ ቦታ ግን ደንበኞቻቸውን ለማግኘት ምቹ ባለመሆኑ በየመንገዱ ለመሸጥ መገደዳቸውን ነጋዴዎቹ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
በከተማዋ ያሉ አንዳንድ እንቁላል አቅራቢ ድርጅቶች አንዱን እንቁላል በ2.50 ብር ሂሳብ ሲሸጡ፣ በየአካባቢው ያሉ ሱቆችና መደብሮች ደግሞ ከ3.00 ብር እስከ 3.50 እየሸጡ ይገኛሉ፡፡ የእንቁላል ዋጋ ከዓምናው የትንሳኤ በዓል ከ1.00 ብር እስከ 1.75 ብር ድረስ ጭማሪ ማሳየቱንም ነጋዴዎችና ሸማቾች ተናግረዋል፡፡
ሽንኩርት በኪሎ ከ12.00 ብር እስከ 12.50 ብር እየተሸጠ ሲሆን ከወትሮው ገበያ እምብዛም የዋጋ ለውጥ እንዳልታየበትና ካለፈው ዓመት ጋርም ተመሳሳይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የቅቤ ዋጋ በአሉን ተከትሎ የጨመረ ሲሆን በአብዛኞቹ ገበያዎች 1ኛ ደረጃ የሚባለው ቅቤ 185 ብር በኪሎ ሲሸጥ፣ ከዚያ በታች የሆኑት ከ165 እስከ 175 ብር በኪሎ እየተሸጡ ነው፡፡
ሳሪስ አካባቢ የበዓል ሸቀጦች ሲሸምቱ ያገኘናቸው ወ/ሮ ፀዳለ ይልማ፤ የትራንስፖርት ዋጋ መቀነሱን ተከትሎ የበዓል ሸቀጦች ዋጋ ቅናሽ እንደሚያሳይ ገምተው እንደነበር ጠቁመው ሆኖም እንደገመቱት ሳይሆን መቅረቱን ተናግረዋል፡፡
ጎተራ መስቀል ፍላወር አካባቢ በጎች ሲሸጥ ያገኘነው ጉልማ ዳዲ፤የበግ ዋጋ ከወትሮው የጨመረው ገበሬው ዋጋ በመጨመሩ ነው ብሏል። ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ ከሚገኘው ፍቼ በጎቹን እንደሚያመጣ የጠቆመው ነጋዴው፤ ገበሬው ካለፈው የገና በዓል በኋላ እንኳ በአንድ በግ ከ150 እስከ 200 ብር ጭማሪ ማድረጉን ገልጿል፡፡
በሾላ ገበያ አስፓልት ዳር በጎቹን ሲሸጥ ያገኘነው ነጋዴም ከደብረ ብርሃንና ለአዲስ አበባ ቅርብ ከሆኑ የኦሮሚያ አካባቢዎች በጎች እያመጣ እንደሚሸጥ ጠቁሞ፤ ገበሬው ከ200 እስከ 300 መቶ ብር የዋጋ ጭማሪ ማድረጉን ተናግሯል፡፡ ያነጋገርናቸው አንዳንድ የበሬ ነጋዴዎች በበኩላቸው፤ በበሬ ዋጋ ላይ ካለፉት በአላት እምብዛም የዋጋ ጭማሪ አለመስተዋሉን ገልፀዋል፡፡
በበአላት ወቅት በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የሚዘጋጁ የጐዳና ላይ የንግድ ባዛሮች  እንደ አንድ የገበያ አማራጭ የሚታዩ ቢሆንም በዋጋ አንፃር ከመደበኛ የገበያ ስፍራዎች ብዙም ለውጥ እንደሌላቸው ሸማቾች ይናገራሉ። ኢንተርፕራይዞቹ ከመንግስት ነፃ የንግድ ቦታ የተመቻቸላቸው እንደመሆኑ ዋጋቸው ከፍተኛ ግብር ከሚከፍሉት ነጋዴዎች እኩል መሆን አልነበረበትም የሚሉት ሸማቾች፤ ለመንግስት ግብር ሣይከፍሉ ህብረተሰቡን በዋጋ መበዝበዛቸው ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡
በለገሃር አካባቢ በተዘጋጀው የንግድ ባዛር ላይ ጫማ ሲገዙ ያገኘናቸው አንድ ሸማች፤ በመደበኛ ቡቲኮች ከ250 እስከ 400 ብር የሚሸጡ ጫማዎች በባዛሮቹም ላይ በተመሳሳይ ዋጋ ሲሸጡ መታዘባቸውን ጠቁመዋል፡፡ የአልኮል መጠጦችም በተመሳሳይ በግሮሰሪዎች ከሚሸጡበት ዋጋ ምንም ለውጥ እንደሌላቸው ሸማቾች ጠቅሰው፤ ባዛሮቹ በመንግስት ድጋፍ የሚዘጋጁ እንደመሆናቸው ዋጋቸው ቅናሽ ማሳየት ነበረበት ብለዋል፡፡ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የተደራጁ ነጋዴዎች በበኩላቸው፣ እንዲህ ያለውን ዕድል የምናገኘው በዓመት ውስጥ ለተወሰኑ ጊዜያት ብቻ በመሆኑ ቅናሽ ማድረግ አያዋጣንም ብለዋል፡፡

Published in ዜና

     የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቻይና በየአመቱ በሚካሄደው “ኢንደስትሪ ጎልደን ቼር አዋርድስ” በተሰኘ አለማቀፍ ሽልማት የዓመቱ ምርጥ አየር መንገድ ተብሎ ለሁለተኛ ጊዜ መሸለሙን አስታወቀ፡፡
አየር መንገዱ ባወጣው መግለጫ እንዳለው፤ ለስምንተኛ ጊዜ በተካሄደውና በአለማቀፍ ደረጃ የላቀ አፈጻጸም ያሳዩ አየር መንገዶች፣ ሆቴሎች፣ የጉዞ ወኪሎችና የቱሪዝም መዳረሻዎች በሚሸለሙበት በዚህ ዝግጅት ተሸላሚ መሆኑ እንደሚያኮራቸው ዋና ስራ አስፈጻሚው አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም ተናግረዋል፡፡
ሽልማቱን ለሚያዘጋጀው ኤምአይሲኢ የተባለ መጽሄት፣ እንዲሁም ለአየር መንገዱ ድምጻቸውን በመስጠት ለተሸላሚነት ላበቁት የቻይና ደንበኞችም ዋና ሥራ አስፈፃሚው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዘመናዊዎቹና በምቹዎቹ 787 እና 777 አውሮፕላኖቹ ቻይና ውስጥ ወደሚገኙት የቤጂንግ፣ የሻንጋይ፣ ጉዋንግዡና ሆንግ ኮንግ መዳረሻዎች በየሳምንቱ በድምሩ 28 በረራዎችን በማድረግ ምርጥና ፈጣን አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡
በዘንድሮው የፈረንጆች አመት ኤር ትራንስፖርት ወርልድ በተባለው ታዋቂ የአቪየሽን ዘርፍ መጽሄት “ቤስት ሪጅናል ኤርላይን” የተሰኘ ሽልማት የተሰጠው አየር መንገዱ፣ ባለፈው አመትም ከአሜሪካ ታዋቂ የጉዞ መጽሄቶች አንዱ በሆነው ፕሪሚየር ትራቭለር “የአፍሪካ ምርጥ አየር መንገድ” ተብሎ መሸለሙንም መግለጫው አስታውሷል፡፡ በ “ፓሴንጀር ቾይዝ” እና በአፍሪካ አየር መንገዶች ማህበርም፣ “ቤስት ኤርላይን ኢን አፍሪካ” እና “አፍሪካን ኤርላይን ኦፍ ዘ ይር” ሽልማቶችን መሸለሙንም አክሎ ገልጿል፡፡

Published in ዜና

    የ1997 ዓ.ም የኮንዶሚኒየም ቤት ፈላጊዎች ምዝገባ ሂደት የተወሳሰቡ ችግሮች የነበሩበት በመሆኑ ለተመዝጋቢዎች የመረጃ ሰነድ መጥፋትና አሁን ድረስ ለዘለቁ በርካታ ቅሬታዎች መነሻ ሆኗል ተባለ፡፡
በወቅቱ ምዝገባው በአዲስ አበባ አስሩም ክፍለከተሞችና በሌሎች ተቋማት የተከናወነ ሲሆን ሁሉም ወገን የምዝገባ ተራ ቁጥሮችን ከ001 የጀመሩ በመሆናቸው መረጃዎቹ ወደ አንድ ማዕከል ሲሰባሰቡ የመደበላለቅ ችግር ፈጥሯል ያሉት የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ሥራ አሥኪያጅ አቶ መስፍን መንግስቱ፤ አንድ ግለሰብ በተለያዩ መዝጋቢ ተቋማት ሶስትና አራት ጊዜ የተመዘገበበት አጋጣሚ እንዳለም ገልፀዋል፡፡
የምዝገባ ማረጋገጫ የነበረውን ቢጫ ካርድ ተመሳሳይ ቁጥር እስከ 15 የሚደርሱ ግለሰቦች ይዘው ወደ ማዕከሉ እንደሚቀርቡ ያስረዱት አቶ መስፍን፤ “ሁሉም መረጃዎች በአንድ ማዕከል ተሰባስበው ከተራ ቁጥር 001 እስከ 453ሺህ ድረስ በመቀመጡ፣ እነሱ ቁጥራችን የሚሉትና ሲስተሙ የሚያውቀው የምዝገባ ቁጥር የተለያዩ ናቸው” ብለዋል፡፡
ለወቅቱ ቤት ፈላጊዎች ምዝገባ እንደ ችግር የተጠቀሰው ሌላው ጉዳይ የ97 ምርጫን ተከትሎ የተፈጠረው ግርግር መረጃን በተገቢው መንገድ ለማደራጀት አለማስቻሉ ነው ይላሉ አቶ መስፍን። በወቅቱ ከተማዋን እንዲያስተዳድር አደራ የተሰጠው የባለአደራ አስተዳደር ስራውን ተላምዶ ወደ ተግባር እስኪገባ ድረስ መረጃዎቹ በተገቢው መንገድ ተይዘው ነበር ለማለት አያስደፍርም ብለዋል - ሃላፊው፡፡
በወቅቱ የተበላሸውን ለማስተካከል በርካታ ስራዎች መሠራታቸውን የጠቀሱት ሃላፊው፤ በ2005 ዓ.ም በተደረገው ምዝገባ፤ “መረጃን ጠፍቶብናል” ያሉ ቤት ፈላጊዎች በነባር የምዝገባ ስርአት ውስጥ ተካተው እንዲስተናገዱ መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
የጋራ መኖሪያ ቤቶች መሠረተልማት ሳይሟላላቸው ለተጠቃሚዎች ይተላለፋሉ በማለት የቤት ባለቤቶች ቅሬታ የሚያቀርቡ ሲሆን የገላን ሶስት ኮንደሚኒየም ነዋሪዎች እስካሁን ድረስ የመብራት አገልግሎት እንደሌላቸው፣ በሌላው የገላን ሳይት ደግሞ የግቢው መንገድ በተገቢው መንገድ ባለመስተካከሉ ለአደጋ የተጋለጡ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ ሃላፊው በበኩላቸው፤ የነዚህ ቅሬታዎች መነሻ ከመሠረተ ልማት ጋር ተያይዞ የነበሩ ክፍተቶች ናቸው ብለዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የቤቶቹ ግንባታ 80 በመቶ ሲደርስ እድለኞች እንዲረከቡ ይደረግ እንደነበር የጠቆሙት ሃላፊው፤ በአሁን ወቅት ግን መቶ በመቶ ተጠናቀውና መሠረተ ልማት ተሟልቶላቸው እንደሚተላለፉ ገልፀዋል። በፊት ለነዋሪዎች መሠረተ ልማት ሳይሟላላቸው የተላለፉትም በአሁን ወቅት ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተሟላላቸው እንደሆነ ሃላፊው ጨምረው ገልፀዋል፡፡ “አካባቢውን ለኑሮ የሚመች ማድረግ ግን የነዋሪው ሃላፊነት ነው” ብለዋል ሃላፊው፡፡
በስም አሊያም በሌላ የማጭበርበር ዘዴ በህገወጥ መንገድ የኮንዶሚኒየም ቤት ተጠቃሚ የሆኑ ግለሰቦች ካሉ ህብረተሰቡ በጥቆማ ማጋለጥ እንደሚገባው ያሳሰቡት አቶ መስፍን፤ እንዲህ ያሉ ችግሮች በተደጋጋሚ  እንደሚያጋጥሙ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡  

Published in ዜና

 ከዚህ በፊትም መታጠቢያ ክፍል ውስጥ ያገኘችውን የአልማዝ ቀለበት ለባለቤቱ መልሳለች
-በኳታር በመታጠቢያ ቤት ውስጥ ያገኘቻቸውን 129 ሺህ ዶላር የሚያወጡ ሁለት የአልማዝ የጣት ቀለበቶች ለባለቤቶቹ ያስረከበችው ኢትዮጵያዊት የጽዳት ሰራተኛ፣ ላሳየችው ታማኝነት በአሰሪዎቿ መሸለሟን ዶሃ ኒውስ ዘገበ፡፡
አንድነት ዘለቀው የተባለችው የ32 አመት ኢትዮጵያዊት የጽዳት ሰራተኛ፣ በምትሰራበት የኳታር ብሄራዊ የስብሰባ ማዕከል መታጠቢያ ክፍል ውስጥ ተረስተው ላለፉት አራት አመታት በማዕከሉ በጽዳት ሰራተኛነት ተቀጥራ ስትሰራ ለቆየችው አንድነት የገንዘብ ስጦታውን ያበረከቱት የማዕከሉ ዋና ስራ አስኪጅ ኬን ጄሚሰን፣ ግለሰቧ ያሳየችው የታማኝነት ተግባር እንደሚያስመሰግናትና ለማዕከሉም ኩራት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ቀለበቶቹን ባገኘችበት ቅጽበት፣ ይሄኔ የቀለበቶቹ ባለቤት እንደጠፋት ስታውቅ ምን ይሰማት ይሆን የሚል ስሜት እንደተሰማትና ባአፋጣኝ ለማዕከሉ ረዳት ስራ አስኪያጅ ደውላ ስለጉዳዩ በመንገር ቀለበቶቹን እንደመለሰች አንድነት ለዶሃ ኒውስ ተናግራለች፡፡ ታማኝነት ታላቁ የህይወት መርህ እንደሆነ አምናለሁ ስትልም ተናግራለች፡፡ አንድነት ከዚህ በፊትም አል ሙክታር በተባለ የኳታር የጽዳት ኩባንያ ውስጥ ተቀጥራ በምትሰራ ወቅት ውድ ዋጋ የሚያወጣ ከአልማዝ የተሰራ የጣት ቀለበት በመታጠቢያ ክፍል ውስጥ ወድቆ አግኝታ ለባለቤቶቹ ማስረከቧን ዘገባው አስታውሷል፡፡
የጣት ቀለበቶቹ ባለፈው የካቲት ወር በማዕከሉ በተካሄደው የዶሃ የጌጣጌጦችና የእጅ ሰዓቶች ኤግዚቢሽን ላይ የጠፉ እንደነበሩ ያስታወሰው ዘገባው፤ ማእከሉ ለኢትዮጵዊቷ የሸለመው ገንዘብ ምን ያህል እንደሆነ አለመገለፁን ጠቁሟል፡፡

Published in ዜና
Page 12 of 17