የለቅሶና የዋይታ ድምፅ በደቡብ አፍሪካ፣ በየመን፣ በሊቢያ…

‹‹. . . ዓይኔ በእንባ ደከመ፣ አንጀቴም ታወከ። ስለ ወገኔ ሴት ልጅ ቅጥቃጤ አንጀቴ በምድር ላይ ተዘረገፈ፡፡ አቤቱ የሆነብንን አስብ፣ ተመልከት ስድባችንንም እይ . . .፡፡››  (ሰቆ. ፪፣፲፩ ፤ ፭፣፩)ይህን ቃል የተናገረው በመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ዘንድ ‹‹አልቃሻው፣ ባለ ሙሾው ነቢይ›› በመባል የሚታወቀው አይሁዳዊው ነቢዩ ኤርምያስ ነው፡፡ ይህንን ነቢይ እንዲህ እንደ ርኁሩኋ እናት አንጀቱን ያላወሰው፣ እንባው እንደ ክረምት ጎርፍ እንዲፈስ ያደረገውና ነፍሱ ድረስ ዘልቆ ብርቱ ኀዘንና ቅጥቃጤን የፈጠረበት ምክንያቱም፡- ኢየሩሳሌም በጠላቶቿ ተማርካ፣ ሕዝቦቿም ተዋርደው፣ ከአገራቸውና ከምድረ ርስታቸው ተነቅለው፣ ያ እጅጉን ያከብሩትና ይፈሩት የነበረው መቅደሳቸው ፈርሶ፣ በግዞት ውስጥ የነበሩትን የሕዝቡን ሰቆቃና መከራ በዓይኑ በማየትና የመከራቸውም ተካፋይ በመሆኑ ነበር፡፡፡ጸሎተኛውና ኀዘንተኛው ኤርምያስ ስለ ኢየሩሳሌም ኃጢአትና በደል፣ በዚህም ስለደረሰባት ከባድ ውርደትና መከራ፣ ዓይኔ ምነው የእንባ ምንጮች ፈሳሽ በሆኑልኝ በማለት የተመኘ፣ በብርቱ የጸለየ፣ የተማጸነና የማለደ የሀገሩ፣ የሕዝቡ ውርደትና ጭንቀት፣ መከራና አበሳ፣ ሰቆቃና ዋይታ እንቅልፍ፣ እረፍት የነሳው ብርቱ የእግዚአብሔር ነቢይ ነበር፡፡ከረሃብ የተነሳ እናቶች የአብራካቸውን ክፋይ ልጆቻቸውን የበሉበትን፣ በቅምጥልነት የኖሩ የኢየሩሳሌም ቆነጃጅትና ደናግል በጠላቶቻቸው ብርቱና ጨካኝ ክንድ ከሰውነት ክብር ተዋርደው፣ ከመፈራትና ከመወደድ የክብር ሰገነት ላይ ተሽቀንጥረው፣ ተንቀውና ተጥለው በጎዳና ያለ ምንም ተስፋ ሲንከራተቱና የሁሉም መጫወቻና ማላገጫ ሲሆኑ ሕፃናት በእናቶቻቸው ደረቅ ጡት ላይ አፋቸው ተጣብቆ በጣእረ ሞት ተይዘው ሲጨነቁ፣ አባቶችና እናቶች የጥንቱን የበረከትና የድሎት ኑሮአቸውን እያሰቡ እንባ ሲቀድማቸው፣ ከክፉ ጠኔ የተነሳ ወላዶች የማኅፀናቸውን ፍሬ እንኳን
ለመብላት ያስጨከናቸውን ያን ክፉ ቀናት የታዘበ ነቢዩ፤ ስለ ቅድስት ምድሩና ሕዝቡ ሰቆቃና መከራ እንዲህ ጸለየ፡- ‹‹እግዚአብሔር ከሰማይ እስኪጎበኝና እስኪመለከት ድረስ ዓይኔ ሳታቋርጥ ዝም ሳትል እንባን ታፈሳለች፡፡›› (ሰቆ ፫፣፵፱፣፶) በማለት በመጮኽና በመቃተት ስለ አገሩ ውርደት፣ ስለ ሕዝቡ መከራ
ሌት ተቀን በእንባ ባሕር እንደዋኘ ውሎ የሚያድር ኀዘንተኛና ሙሾ የሚደረድር ነቢይ ነበር፤ አይሁዳዊው የእግዚአብሔር ሰው ኤርምያስ።ሰሞኑን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ሁሉ እንደ አይሁዳዊው ነቢይ ኤርምያስ አንገታችንን የሚያስደፋና በሃፍረት የሚያሸማቅቅ፣ ጆሮን ጭው የሚደርግ፣ የወላድ እናቶችን አንጀት
የሚያላውስና በእንባ ጎርፍ እንዲታጠቡ የሚያደርግ ሌላ የሞት፣ ሌላ የውርደት፣ መሪር መርዶ፣ ሰቅጣጭና ክፉ ዜና ለእናት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ምድር፣ ከሊቢያ፣ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከሀገረ የመን ተሰምቷል፡፡በእርግጥ የአገራችንና የወገናችን ውርደትና መከራ ገና ዛሬ የተጀመረ አይደለም። በርካታ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ዓለምን ሁሉ እግዚኦ ካሰኘ ድርቅ፣ የረሃብ/የጠኔ እልቂት እስከ የወንድማማቾች የእርስ በርስ ደም መፋሰስ፣ ዘግናኝ ጦርነትና ፍጅት ድረስ የሕዝባችን ስደት፣ መከራና ውርደት የአገራችን ዋንኛ መለያ ሆኖ አብሮን ለዓመታት ዘልቋል። በዓለም ሁሉ ፊት ኢትዮጵያዊነት ብዙዎችን እንዲሳቀቁ ያደረጋቸው “አሳፋሪ” ማንነት የሆነበትን ጥቁር ታሪካችንን ዛሬም ገና በቅጡ ልንላቀቀው እንዳልቻልን እያየን፣ እያስተዋልን ነው፡፡ስደትና ውርደት፣ መከራና ሞት የሕዝባችን ዕጣ ፈንታ እንዲሆን የተፈረደበት ይመስል ዛሬም ምስኪን ሕዝባችን በሚሰቀጥጥ ሁኔታ የአውሬ፣ የበረሃና የባሕር ሲሳይ እየሆነ ነው፡፡ በለስ ቀንቶት ወደ ባዕድ ምድር የገባው ሕዝባችንም ከእንስሳ በወረደ ሁኔታ ሰብአዊ ክብሩ ተደፍሮና ተዋርዶ፣ የሞት ሞት እንዲሞት የተደረገበትን አጋጣሚዎችንም ደግመን ደጋግመን ታዝበናል፡፡ በሳውዲ አረቢያ ሊያውም በአገራችን ኤምባሲ ፊት ለፊት አስክሬኗ በመኪና መሬት ለመሬት እንዲጎተት የተደረገበትን ያን አንገታችንን ያስደፋንን የወገናችንን ውርደት መርሳት እንዴት ይቻለናል?!በመካከለኛው ምሥራቅ ከፎቅ ላይ የሚወረወሩ፣ የፈላ ውሃ የሚደፋባቸው፣ አሰቃቂ የሆነ ግፍና ውርደት የሚፈጸምባቸው… የእህቶቻችን ሰቆቃና መከራ ዛሬም ማብቂያ የተገኘለት አይመስልም። በኬንያ፣ በታንዛንያ፣ በማላዊና በሞዛምቢክ እንዲሁም በመካከለኛው ምሥራቅ “ሕገ ወጥ” ናችሁ በሚል ሰበብ በእስር ቤት ታጉረው ፍዳ መከራቸውን እየቆጠሩና “የወገን ያለህ ደረሱልን” እያሉ
የሚገኙ ወገኖቻችን ቁጥርም ቀላል አይደለም።በቅርቡም በደቡብ አፍሪካ ምድር ወገኖቻችን በቁማቸው በእሳት እንዲጋዩ፣ በቆንጨራና በጥይት ተደብድበው እንዲገደሉ ተፈረደባቸው። ጥረው ግረው፣ ለፍተውና ደክመው ያከማቹት ሀብት ንብረታቸውም የዘራፊዎች ሲሳይ ሆነ። ይሄ ያደረሰብንን ጥልቅ ሃዘን በቅጡ ሳንወጣ ዳግመኛ ልባችንን በኀዘን ጦር የወጋ፣ ጆሮን ጭው የሚያደርግ ክፉ ወሬ ከወደ ሊቢያ ምድር ሰማን፡፡ 28
የሚሆኑ ወገኖቻችን በሊቢያ በረሃ ዘግናኝ በሆነ አኳኋን በግፍ ታርደው ሰማዕትነትን መቀበላቸውን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን አረዱን፡፡በንጉሥ ሄሮድስ ዘመን ለተፈጁት 14 ሺ አይሁዳውያን ሕፃናት ነቢዩ ኤርምያስ፡- ‹‹የጩኸት፣ የጣርና ሰቆቃ ድምፅ በራማ ተሰማ፣ ራሄል ስለ ልጆቿ አለቀሰች የሉምና፡፡›› እንዳለው ዛሬም ከመካከለኛው ምሥራቅ፣ ከየመን፣ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከሊቢያ… ምድር የልጆቿን ጩኸት፣ ሰቆቃና ዋይታ የሰማች እማማ ኢትዮጵያም ማቅ ለብሳ፣ ትቢያ ነስንሳ ሙሾን እያወረደች ነው፡፡ የልጆቿ ኀዘን፣ ሰቆቃና ዋይታ ገና በቅጡ ያልታበሰላት ምድር፤ ዛሬም ዕጣ ፈንታዋ ዕንባና ደም፣ ሰቆቃና ዋይታ ሆኗል፡፡መንግሥት ሕዳሴዋ በደጅ ነው፣ ልማቷና ዕድገቷም እየተፋጠነ ነው ቢልም አገራችን ዛሬም ለልጆቿ ጥላና ከለላ ለመሆን የቻለች አይመስልም። ከሳዑዲ አረቢያ ውጡልን ተብለው ወደ እናት አገራቸው ተመልሰው ከነበሩ እህቶቻችን መካከል “ከዚህስ ኑሮ ብንሞትም ብንድንም እዚያው አረብ አገር ይሻለናል” በሚል ተስፋ ቆርጠው ዳግመኛ በመጡበት እግራቸው ሲመለሱ ታዘበናል፡፡የብዙዎች ወገኖቻችን እንባና ደምም ለለውጥና ለአዲስ ተስፋ በሀገራችን ተራሮችና ሸንተረሮች እንደ ውሃ ፈሷል፡፡ የአንድ ማኅፀን አብራክ ክፋዮች እርስ በርሳቸው ተራርደዋል፣ ተላልቀዋል። ብዙዎቻችንም ነፍሳችን እስክትዝል ለሀገራችን ለውጥ በብዙ አንብተናል፣ ወጥተናል ወርደናል፡፡
የለውጥ ያለህ በሚል፣ ከልብ በሆነ ናፍቆትም ነደናል፣ ተቃጥለናልም፡፡ ዛሬም በናፍቆት እንደተቃጠልን፣ እንደ ሽንብራ እንደተርገበገብን፣ በናፍቆት ነፍሳችን እንደዛለች መሽቶ ይነጋል፡፡ይህችን በለውጥ ናፍቆት፣ የተስፋ ጭላንጭል ያለህ በሚል የዛለች ነፍሳችንን አይዞሽ የሚሏት፣ የውስጣችንን ጩኸት የሚመልሱ፣ ስብራታችንን የሚጠግኑልን፤ ታሪካችንን፣ የሚያድሱልንና ለነገ ብሩህ ተስፋ ሊያሳዩን የሚችሉ ደጋግ፣ ሁሉን በፍቅር የሚያዩ መሪዎች፣ ፖለቲከኞች፣ የሃይማኖት መሪዎችና መንፈሳዊ አባቶች እንዲኖሩን ደጋግመን ተመኝተናል፡፡ ግና እምብዛም አልተሳካልንም፡፡ ተስፋችን ያዝነው ስንለው እያመለጠን፣ ጉልበታችን ዝሎ ከዚሁ የዘመናት እንቆቅልሾቻችን፣ ያለ ቅጥ ከረዘመው የጨለማው ዘመን ዥንጉርጉር ታሪካችን፣ ጉስቁልናና ውርደት ከተሞላው አስከፊ ገጽታችን ጋር አብረን እየተጓዝን እዚህ ደርሰናል፡፡“አቤቱ እባክህ የሆነብንን አስብ፣ ተመልከት ስድባችንንም እይ . . .፡፡››
ሰላም! ሻሎም!

“ሙስሊም ባልሆኑ ንፁሃን ሰዎች ላይ ግድያ የፈፀመ ሰው የጀነትን እጣን አያሸትም”

   በሁለቱ ታላላቅ እምነቶች ውስጥ (ክርስትና እና እስልምናን ማለቴ ነው) ለሰው ዘር በሙሉ የተላለፈ አንድ መለኮታዊ መልዕክት አለ፡፡ ይህ መልዕክት በሁለት ቅዱሳን መፃህፍት ውስጥ ቢገኝም መልዕክቱ ግን ተመሳሳይ ነው፡፡ የሰው ልጅን ነፍስ ማጥፋት የተወገዘ ተግባር መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ እና ቁርአን ያወሳሉ፡፡ ይህን መልዕክት ለሰው ልጆች የላከው ደግሞ የሰማይና የምድር ፈጣሪ እንዲሁም የሰው ልጆችን ጨምሮ በሁለቱ መካከል ያሉትን በሙሉ ያስገኘው አምላክ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ምዕራፎቹ ውስጥ የሰው ልጅ ግድያን ይከለክላል፡፡ በማቲዎስ 5፡21፣ ምፅአት 20፡13፣ ሮሜ 13፡14፣ ዘፍጥረት 9፡5-6 … ወዘተ፤ በጣም ብዙ አንቀፆች ሰውን መግደል የማይፈቀድ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በማቲዎስ 5፡21 ውስጥ የሰፈረው ቃል እንዲህ ይላል፡-
“… አትግደል፤ የገደለ ሰው ይፈረድበታል …”
በቅዱስ ቁርአን ውስጥም የሰው ልጅን ነፍስ ማጥፋት ትልቅ ሀጢአት መሆኑ በብዙ አንቀፆች ውስጥ ፍሮአል፡፡ በአል-ሙምታሐና፡8፣ በአል-ኒሳ 89—91፣ በአል-በቀራ፡ 190፣ በአል-አንኢም፡151…
ውስጥ የመግደልን አስከፊነት ያነሳል፡፡ በአል-ማኢዳ፡32 ውስጥ የሰፈረው እንዲህ ይነበባል፡- “… አንድ ነፍስን የገደለ ሰው መላውን የሰው ዘር እንዳጠፋ ይቆጠራል፤ አንድ ነፍስን ያዳነ ሰው መላውን የሰው ዘር እንዳዳነ ይቆጠራል…”
በእስልምናም ሆነ በክርስትና እምነቶች ውስጥ የመግደልን አስከፊነት የሚገልፁ የአምላክ ቃላቶች ተቀምጠዋል፡፡ ምዕመናን ከዚህ ክፉ ተግባር እንዲቆጠቡም ሐያሉ አምላክ አዟል፡፡ ነገር ግን በእስልምናም ሆነ በክርስትና ሐይማኖት ተከታዮች በርካታ የግድያና የሽብር ተግባሮች መፈፀማቸውን ታሪክ ይነግረናል፡፡ እንደ ፖለቲካ ተመራማሪዎች ከሆነ፤ የሽብርተኝነት ዋና አላማ በመንግስት አልያም በሆነ አካል ላይ ተፅዕኖና ማስገደድን መፍጠር ነው፡፡ ሽብርተኝነት ከማንኛውም ሀይማኖት ጋር የሚገናኝ አይደለም። አንዳንድ ጊዜ ፍትህ ያጡ ግለሰቦች የሚከተሉት ተግባር ሲሆን ሌላ ጊዜ ደግሞ የፖለቲካ አላማን ያነገቡ ቡድኖች ፈፅሙት ነው፡፡ ሃይማኖቶች መግደል ክልክል መሆኑን የሚገልፁ ከሆነ ታዲያ ለምንድነው ሃይማኖተኞች የሚገድሉት? ግድያና ሽብር ማካሄድ የሚገናኘው ከሃይማኖት ጋር ነው ወይስ ከፖለቲካ? የተለያዩ እምነቶችን የሚያራምዱ የአለማችን ሰዎች በደርዘን የሚቆጠሩ ግድያና ሽብሮችን በንፁሐን ዜጎች ላይ ፈፅመዋል፡፡ ለምሳሌ በ2011 ዓ.ም የቀኝ ክንፍ ክርስቲያን አክራሪ የሆነው አንደርስ ብሪቬክ በኖርዌይ 77 ሰዎችን ገድሏል፡፡ ብሪቬክ ከፍተኛ የሆነ የእስልምና ሃይማኖት ጥላቻ እንደነበረው በወቅቱ ተገልጿል፡፡ በ2013 ዓ.ም የሶማሊያ ሙስሊሞች በዌስትጌት የገበያ ሞል ውስጥ ቦንብ አፈንድተው የ67 ሰዎችን ህይወት ቀጥፈዋል፡፡ በ1955 ዓ.ም በኦክላሐማ ከተማ ውስጥ የፈነዳው ቦንብ 166 ንፁሐንን ገድሏል፡፡ ድርጊቱን የፈፀሙት ደግሞ ቲሞቲ እና ቴሪ የተባሉ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ በ2002 ዓ.ም በባሊ ደሴት ላይ የፈነዳው ቦንብ የ202 ዜጎችን ነፍስ በልቷል፡፡ ድርጊቱን የፈፀሙት ጀማህ ኢስላሚያ የተባሉ የእስልምና ተከታዮች ናቸው፡፡ በ2004 ዓ.ም የሰሜን ምስራቅ ህንድ ክርስቲያኖች ድርጅት 44 ሰዎችን ገድሏል፡፡ በ2001 ዓ.ም የተጠለፈ አውሮፕላን በዓለም የንግድ ድርጅት ህንፃ ላይ ተጋጭቶ 3000 ንፁሐንን ገድሏል፡፡ ተግባሩን የፈፀሙት የአልቃኢዳ ሙስሊሞች ነበሩ፡፡
በ2015 በጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የአል-ሻባብ ሙስሊሞች 148 ኬንያውያንን ገድለዋል፡፡
በ1972 ዓ.ም የካቶሊክ እምነት ተከታዮች የሆኑት የአይሪሽ ሪፐብሊካን አርሚ ቡድኖች በለንደን 47 ሰዎችን በቦንብ ፈጅተዋል፡፡ እነዚህን የመሰሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሽብርና ግድያዎችን በሁለቱም እምነቶች ውስጥ የሚገኙ ቡድኖችና ግለሰቦች ፈፅመዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው ደግሞ ሽብርና ግድያ ባለቤትነቱ የማንም ሃይማኖት አለመሆኑን ነው፡፡ የቀድሞ የግብፅ ሙፍቲ ሼክ አሊ ጎማኢ እንደተናገሩት፤ “ሽብርተኝነት ሃይማኖት የሚወልደው ጉዳይ አይደለም፡፡ ሽብርተኝነት የብልሹ አስተሳሰብ ውጤት ነው፡፡ ሽብርተኝነት፣ የእብሪተኝነትና አጥፊነት መገለጫ ነው፡፡ ብልሹነት፣ እብሪተኝነትና አጥፊነት ከመለኮታዊ ልቦና ጋር የሚገናኙ አይደሉም፡፡” ራሱን የእስልምና መገለጫ አድርጎ የሚንቀሳቀሰው አይሲስም የግብፁ ሙፍቲ በተናገሩት ውስጥ የሚፈረጅ መሆኑን ተግባራቱ ያሳያሉ፡፡ ባለፈው እሁድ በ28 ኢትዮጵያውያን ላይ የተፈፀመው አሰቃቂ ግድያ አላማው ግልፅ አይደለም፡፡ አይሲስ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ምን አይነት ቅያሜ ውስጥ ቢገባ ይሆን 28 ዜጎቿን የፈጀው? ለሚለው ጥያቄም መልስ የለውም። አይሲስ የገደላቸው
ኢትዮጵያውያን ክርስቲያን በመሆናቸው ብቻ ነው እንዳንል በማግስቱ 24 የኢራቅ ሙስሊሞችን ገድሏል፡፡ ለዚህም ነው የአይሲስ አላማና መገለጫ የግብፁ ሙፍቲ ከተናገሩት ጋር ይገናኛል ያልኩት፡፡ አይሲስ ሙስሊም ክርስቲያን ሳይል በሰው ዘር ላይ የዘመተ አረመኔ ቡድን መሆኑ አያጠራጥርም፡፡
አይሲስ የሸሪአ ተከታይ ነው ከተባለ ለምንድነው ታዲያ በቁርአን ውስጥ የሚገኘውን አል-ማኢዳ፡32
የጣሰው? “አንድ ነፍስን ያጠፋ መላውን የሰው ዘር እንዳጠፋ ይቆጠራል፤ አንድ ነፍስን ያዳነ መላውን የሰው ዘር እንዳዳነ ይቆጠራል፡፡” የሚለው መለኮታዊ ቃል ለምንድነው በአይሲስ ያልተከበረው? የሰው ነፍስን  አጥፍቶ ጀነትን መመኘት የዋህነት ይመስለኛል፡፡ በታላቁ መምህር በነብዩ ሙሀመድ የህይወት ፈለግ ውስጥ የዚህ አይነቱ ርዕዮት በፍፁም የተወገዘ ነው፡፡ በቡካሪ ሐዲስ ውስጥ ነብዩ ሙሀመድ የተናገሩት ይህን ይመስላል፡-
“ሙስሊም ባልሆኑ ንፁሐን ሰዎች ላይ ግድያ የፈፀመ ሰው የጀነትን እጣን አያሸትም” ንፁሐን ሰዎች ላይ ግድያ ፈፅመን ጀነት መግባት የምንመኝ ከሆነ ካሁኑ እርማችንን ማውጣት አለብን፤ ነብይ ሽታውን እንኳን እንደማናገኘው አርድተውናልና፡፡ በእስልምና ሐይማኖት ውስጥ ጥልቅ እውቀት ያለው አይሲስ ወይስ መልእክተኛው ሙሐመድ? አይሲስ የሚያራምደው እስልምና ከየት የመጣ ይሆን? ነብዩ ካስተማሩትና ካዘዙት የእስልምና እውቀት ውጭ ከየት ሊመጣ!

    ባለፈው እሁድ ከሊቢያ ወደ ጣሊያን ከ900 በላይ የተለያዩ አገራት ስደተኞችን አሳፍራ ስትጓዝ በሜዲትራኒያን ባህር የመስጠም አደጋ በደረሰባት ጀልባ ከሞቱት መካከል አንዱ በአዲስ አበባ የኮተቤ ነዋሪ የነበረው እንዳልካቸው አስፋው ይገኝበታል፡፡ በታክሲ ረዳትነትና ሹፌርነት ይተዳደር የነበረው እንዳልካቸው፤ ኑሮን ለማሸነፍ የተሻለ ስራ ፍለጋ የዛሬ 6 ዓመት ወደ ሱዳን ማቅናቱንና እዚያ ለ5 ዓመታት ከቆየ በኋላ ከዓመት በፊት ሊቢያ መድረሱን ደውሎ እንዳሳወቃቸው ቤተሰቦቹ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ “ለረጅም ጊዜ ድምፁ ጠፍቶብን ነበር” የሚሉት ቤተሰቦቹ፤ በሊቢያ ያለው ሁኔታ አስጨናቂ እየሆነ ከመጣበት ጊዜ አንስቶ በሃሳብና በሰቀቀን ‹እንዴት ሆኖ ይሆን?› እያሉ ድምፁን ለመስማት በመናፈቅ ወደ ፈጣሪያቸው ይለማመኑ እንደነበር ይገልፃሉ፡፡ በመጨረሻቡ ባልጠበቀው ሁኔታ እንደወጣ የቀረውን የእንዳልካቸውን ህልፈት የሰሙት ባለፈው ረቡዕ መሆኑን ወንድሙ ሙሉጌታ አስፋው ተናግሯል፡፡ የእንዳልካቸውን ህልፈት በስልክ ለቤተሰብ ያረዱት ለቀጣዩ የባህር ጉዞ ተረኛ የነበሩና እርሱን በቅርበት የሚያውቁት ስደተኞች ናቸው፡፡ “ወንድማችን ሱዳን ውስጥ ሲኖር የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ ራሱን ያስተዳድር ነበር” የሚለው የሟች ወንድም፤ ባጠራቀመው ገንዘብ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ወደ አውሮፓ ለመሻገር ጥረት ሲያደርግ ባደረገበት አጋጣሚ ከቤተሰቡ እንደተነፋፈቀ መቅረቱ ለቤተሰቡ መሪር ሀዘን እንደሆነበት ተናግሯል፡፡ “ዴይሊ ሜይል” ጀልባዋ 950 ኤርትራዊያን፣ ኢትዮጵያውያንና ሶማሊያውያን ስደተኞችን አሳፍራ ስትጓዝ መስጠሟን የዘገበ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 200 ያህሉ ሴቶች እንደነበሩ ጠቁሟል፡፡ ከአደጋው የተረፉት 28 ብቻ መሆናቸውን የዘገበው ጋዜጣው፤ ሲሆኑ አስክሬናቸው የተገኘው የ20ዎቹ ብቻ ነው ብሏል፡፡ “አልጀዚራ” እና “ዘ ጋርዲያን” በበኩላቸው ጀልባዋ 700 ስደተኞችን አሳድራ እንደነበር ጠቁመውየተረፉት 28 አስከሬናቸው የተገኘው 20 ብቻ መሆኑን ዘግበዋል፡፡ አደጋው የተፈጠረው በጀልባዋ ላይ ተፋፍገው የተጫኑት ስደተኞች በርቀት ሌላ የንግድ መርከብ
ተመልክተው ጥሪ ለማቅረብ ሲሉ በፈጠሩት ግርግር ጀልባዋ ሚዛኗን በመስጠሟ ነው ብለዋል ዘገባዎች፡፡
ከአደጋው የደረሰው ከሊቢያ የባህር ዳርቻ 96 ኪ.ሜ እንዲሁም ከጣሊያኗ የስደተኞች መዳረሻ
ላምፔዱሣ ደሴት 193 ኪ.ሜ ርቀት ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡

Published in ዜና

በሊቢያ ከተገደሉት ውስጥ 5ቱ የጨርቆስ ወጣቶች ናቸው
ልጆቻቸው ሊቢያ የሄዱባቸው ወላጆች በጭንቀት ተወጥረዋል  
   በደቡብ አፍሪካ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ በደረሰው ዘረኛ ጥቃት ማግስት፣ በሊቢያ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ላይ የተፈፀመው የአሸባሪ ቡድኑ አይኤስአይኤስ  ዘግናኝ ግድያ፤ የኢትዮጵያውያንን ሐዘንና ቁጭት መራር አድርጎታል፡፡ እስካሁን የዘጠኙ  ሟቾች ማንነት የታወቀ ሲሆን ቤተሰቦች መርዶ ተነግሯቸው፣ ለቅሶ መቀመጣቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ወላጆችና ቤተሰብ፣ ወንድምና እህት፣ ጎረቤትና ወዳጆች ሁሉ ውስጥን በሚያደማ ቅፅበታዊ ሐዘን ተመተዋል።    በሊቢያ የአሸባሪው ቡድን ‘አይኤስአይኤስ’ ታጣቂዎች ’30 ኢትዮጵያዊያን ክርስትያኖችን ገድለናል’ ብለው አሰቃቂ የግድያ ቪዲዮና ፎቶ ማሰራጨታቸውን ተከትሎ፣ ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦች መርዶ ሲደርሳቸው ነው የሰነበቱት። እስካሁን በደረሰን መረጃ፤ በሊቢያ ከተገደሉት ውስጥ 5ቱ የጨርቆስ ወጣቶች ሲሆኑ ከትግራይ አንድ፣ከወለጋ ሁለት እንዲሁም ከሐረርጌ አንድ ኢትዮጵያውያን መገደላቸው ታውቋል፡፡ ከወለጋ የመንግስቱ ጋሼና የአወቀ ገመቹን እንዲሁም ከሐረርጌ “ከክርስቲያን ወገኖቼ አልለይም” በማለቱ አብሯቸው ተገድሏል የተባለውን የጀማል ራህማን  ቤተሰቦች ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡ ባለፈው ሰኞ  የጓደኛሞቹ ኢያሱ ይኩኖአምላክ እና ባልቻ በለጠ መርዶ የተነገረ ሲሆን በቀጣዮቹ ቀናት የሌሎች ሦስት ወጣቶች መርዶ ለየቤተሰቦቻቸው ተነግሯል፡፡ ሟቾቹ ኤልያስ ተጫነ፣ ብሩክ ካሣና  በቀለ ታጠቁ ናቸው፡፡ በሰላሳዎቹ ዕድሜ ላይ የነበሩት ኢያሱና ባልቻ፤ጨርቆስ ውስጥ ያደጉ ጎረቤታሞች ሲሆኑ ከሁለት ወራት በፊት በሊቢያ አድርገው ወደ አውሮፓ ለመሻገር ወጥነው ነበር
ጉዞ የጀመሩት፡፡ ነገር ግን በሊቢያ አሸባሪ ቡድን ‘አይኤስአይኤስ’ በግፍ ተገደሉ፡፡  አቶ ካሳ አግና የ24 አመቱ ወጣት ብሩክ ካሳ አባት ናቸው፡፡ ልጃቸው ከቤት ከወጣ ሶስት ወር እንደሞላው ይናገራሉ፡፡ “ተግባረእድ መማር ጀምሮ ነበር፤ሆኖም ስድስት ወር ሳይሞላው ተወውና ከኔ ጋር ሱቅ መስራት ጀመረ፡፡ አንድ ቀን ሱቅ ሲሰራ ውሎ ማታ የዘጋበትን ቁልፍ እንኳን ሳይሰጠን ጠፋ። መተማ ሲደርስ ነው የነገረን፤ ሱዳን ላይ ደወለ፣ ከዚያም ሊቢያ ሲደርስ  ስልክ ሰጥቶኝ ስለነበር ስደውልለት ገንዘብ ያስፈልገኛል አለኝና  ላኩለት፤ ከዚያ በኋላ ግን አልደወለም፡፡” ይላሉ የሟች ብሩክ አባት፡፡ አቶ ካሣ ባለፈው ረቡዕ የአሸባሪው ቡድን ‘አይኤስአይኤስ’ ን አረመኔያዊ ተግባር ለማውገዝ በተጠራው ሰልፍ ላይ ተገኝተው ነበር፡፡ እዚያው ሳሉ ከልጃቸው ጋር ሊቢያ የሄደው ጓደኛው ሞቷል ተብሎ ተነገራቸውና ሰልፉን አቋርጠው ወደ ሰፈር ሄዱ፡፡ “እዚያ ስደርስ የእኔንም ልጅ መርዶ ነገሩኝ” ያሉት አቶ ካሣ፤ “እኔ አይቼ አላረጋገጥኩም፤ የሰፈር ልጆች ግን አብረውት ስለሚውሉ እሱ
መሆኑን  በፌስ ቡክ ማረጋገጣቸውን ነግረውኛል” ብለዋል፡፡ ከትናንት በስቲያ በለቅሶው ላይ የተገኙ አንድ የሰፈሩ ነዋሪ፣ የብሩክ እናት ከአንድ ወር በፊት ጠበል ሊቀምሱ መጥተው ሰዉን “እባካችሁ ሆዴ እየተረበሸ ነው፤ ልጄ ብድግ ብሎ ሄዷል፤ በፀሎታችሁ አትርሱኝ” ማለታቸውን በሀዘን ያስታውሳሉ፡፡ አቶ ተጫነ ዘለቀ የ24 አመቱ ወጣት ኤልያስ አባት ናቸው፡፡ እድሜያቸው የገፋ አዛውንት ሲሆኑ እሳቸውም ልክ እንደ አቶ ካሳ የሰፈር ልጆች “በመልክ ለይተን ምስሉን አግኝተናል” ባሏቸው መሰረት የልጃቸውን ሞት እንደተረዱ ይናገራሉ፡፡ ልጃቸው ከአገር ለመውጣት ማሰቡን ሲነግራቸው፣“በዚህ  በእርጅና እድሜዬ ምነው ጥለኸኝ ትሄዳለህ” አሉት፤ “አይ እሄዳለሁ፤ እዚህ ምንም አላለፈልንም፤ እዛ ሄጄ ትንሽ እሞክራለሁ” ብሎ መሄዱን አባት ተናግረዋል። ሊቢያ እስኪገባ ድረስ በስልክ እንገናኝ ነበር፤ በኋላ ግን ጠፋብን ፤ልጆቼ በፌስቡክ ቢፈልጉትም ሊያገኙት አልቻሉም፤ ያለበትን እያፈላለግን ሳለ ይሄ መአት ወረደብን” ብለዋል በሃዘን ተውጠው፡፡  አሸናፊ ቦጋለና ውድነህ ታደሰ  የሟቾቹ  የኤሊያስና የብሩክ አብሮ አደጎች  ናቸው፡፡ ከመሄዳቸው
አንድ ቀን በፊት ማታ ብሩክን ወደ ቤት ሲገባ አግኝተነው፤ “እንዲህ -- ሰምተናል” ስንለው፣ “አዎ
አስቤያለሁ” አለን፡፡ ኤሊያስ ግን እንደሚሄድ ነግሮን፣ መልካሙን ሁሉ ተመኝተንለት ነበር የተሰናበትነው፡፡ ደስታና ሀዘን አብረን ያሳለፍን ጓደኞቻችን ናቸው፤ረቡዕ ጠዋት ሰለማዊ ሰልፉን ለመውጣት ስንዘጋጅ አንድ የሰፈራችን ልጅ፣ “ሁለቱ ልጆች በአይኤስአይኤስ ቡድን ሲገደሉ በግልፅ የሚያሳይ ምስል አየሁ” ብሎ አሳየን፤ግን አላመነውም፤ ሌላ የሰፈራችን ልጅ ፊልሙን በኮምፒዩተሩይዞ መጥቶ “ይህ ጓደኛችሁ አይደለም ወይ?” ብሎ አሳየን፡፡ መጀመሪያ ኤሊያስን አየነው፡፡ ቀጥሎ ሁሌም አቀርቅሮ በመሄድ የሚታወቀው ብሩክ፤ በምስሉም ላይ ከገዳዮቹ ስር አቀርቅሮ አየነው፤ብለዋል፡፡  “በጓደኞቻችን ላይ የተፈጠረው ነገር ልባችንን እጅግ ሰብሮታል፤ ቃላት ከሚገልፁት በላይ አዝነናል። አይደለም በምንወዳቸው፣ ጥምቀትን አብረን የምናሳልፍ ጓደኞቻችን ላይ ቀርቶ በግብፃውያኑ ላይ የተፈጠረውም እጅግ አሳዝኖናል፡፡ ኤሊያስም ሆነ ብሩክ ብዙም የመሄዱ ሀሳብ አልነበራቸው፤ እገሌ እዚህ ገባ፣ እከሌ እዚህ ደረሰ የሚሉ ወሬዎች አነሳስተዋቸው መሆን አለበት” ብለዋል የሟቾቹ ጓደኞች፡፡ ከጉራጌ አካባቢ መጥቶ ጨርቆስ ያደገው በቀለ ታጠቁ ወይም በቀለ አርሴማ እድሜው 20 መሆኑን  የአካባቢው ሰዎች ይናገራሉ፡፡ በቀለ እዚያው ጨርቆስ ፖሊስ ጣቢያ አካባቢ በሚገኝ የሞባይል ቤት ተቀጥሮ ይሰራ ነበር፡፡ የበቀለ ቤት ከኤሊያስና ከብሩክ መኖሪያ ብዙም ባይርቅም ከአገር አብረው ባይወጡም ስደት ላይ ተገናኝተዋል፡፡ የበቀለ መርዶም ቤተሰቦቹ ወዳሉበት ጉራጌ ዞን ደርሷል፡፡ ለጨርቆስ ነዋሪዎች የሰሞኑ መርዶ እርም ማውጣት ብቻ አይደለም፤ “ቀጥሎ ማን ይሆን ተረኛ?”
የሚል ስጋት ያዘለ ነው፤ ይላሉ ነዋሪዎች። ሀዘንተኞቹ ቤት እየመጡ ከሚያለቅሱ የሰፈሩ ሰዎች በርካታዎቹ  የልጆቻቸውን ቁርጥ አላወቁም-ይኑሩ ይሙቱ በጥርጣሬ ውስጥ ናቸው፡፡ ወሬው ሁሉ የስጋት ነው፡፡ “እከሌ ሄዷል፤ እዚህ ፎቶ ላይ አልታየም ነገርግን ድምፁ ከጠፋ ቆይቷል፤ የእከሌ መርዶ ሊነገር ነበር ፤ ፎቶውን እርግጠኛ ስላልሆንን ተውነው፤የእከሌ ልጅ ካምፕ ነኝ ብሏል፤ እነእከሌን ግን ማግኘት አልቻለም” እያሉ ጥርጣሬያቸውን ይተነፍሳሉ፡፡  ልጆቻቸው ወደ ሊቢያ የተሰደዱባቸው ቤተሰቦች፣ ነገን በስጋትና በፍርሃት ነው የሚጠብቋት፡፡ ምን ይዛላቸው እንደምትመጣ እርግጠኛ አይደሉም፡፡ ከሁሉም አሳዛኙ ደግሞ ልጆቻቸው በስደት መሞታቸው እየታወቀ ቢነገራቸው በድንጋጤ አንድ ነገር እንዳይሆኑ በሚል ፍራቻ ፣ከዛሬ ነገ የልጄን ድምፅ እሰማለሁ እያሉ በተስፋ የሚኖሩ ወላጆች መኖራቸው ነው፡፡ በትግራይ ክልል በማእከላዊ ዞን አህፈሮም ወረዳ በምትገኘው የእንትጮ ከተማ ነዋሪ የነበረው ዳንኤል ሀዱሽ  ሌላው የሊቢያው አሸባሪ ቡድን የጥፋት ሰለባ ነው፡፡ የ25 አመቱ ወጣት ዳንኤል፣ ባለፈው አመት ከጅማ ዩኒቨርሲቲ በኮምፒዩተር ሳይንስ ተመርቋል። በተማረበት ሙያ ሥራ ሲያፈላልግ እንደነበር ቤተሰቦቹ ይናገራሉ፡፡ በመጨረሻ  ለወላጅ እናቱ ለወይዘሮ ዛፉ ገብረእየሱስ፣ ሁመራ ስኳር ፋብሪካ ስራ እንዳገኘ በመንገር ነበር  ጥር 25 ቀን 2007 ዓ.ም የተለያቸው፡፡ ከቀናት በኋላም “ያለሁበት ቦታ የኔትወርክ ችግር ስላለ እኔ ካልደወልኩኝ አታገኙኝም” ማለቱን፣ ከዚያም
ሊቢያ መግባቱን ለእናቱ ደውሎ እንደነገረ ቤተሰቡ ይገልጻል፡፡ የዳንኤልን መልክ በፎቶ ለመለየት
የሚያስቸግር እንዳልሆነ የተናገሩት ምንጮቻችን፤ ከትላንት በስቲያ ለእናቱና ሌሎች ቤተሰቦቹ
መርዶው ተነግሮ፣ በእንትጮ ማርያም ደብረገነት ፍትሀት እንደተደረገለትም ጠቁመዋል፡፡  በፌስቡክ ምስል በማየት ሞትን  ማርዳት  ልጆቻቸውን ያጡትንም ሆነ ሌሎች በስጋት ላይ ያሉትን ሙሉ በሙሉ ላያሳምን  ይችላል የሚል ጥርጣሬ ቢፈጠርም  ወላጆች የሰፈር ልጆች አይተናል ባሉት የምስል መረጃ ነው ሀዘን የተቀመጡት፡፡ አንድ የመቀሌ ወጣት ከሟቾቹ አንዱ እንደሆነ ተደርጎ በፌስቡክ የተለጠፈውን ፎቶውን እያስተባበለ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡ ሆኖም በስደት ላይ ያለ ሰው ለማፈላለግ ከፌስቡክ የተሻለ መንገድ አልተገኘም፡፡ በዚህም የተነሳ ወደ ሊቢያ የሄደ ሰው ያላቸው
ቤተሰቦች በፌስቡክ ፎቶውን በመለጠፍ አፈላልጉን እያሉ ነው፡፡   

Published in ዜና
  • ከ2 ዓመት በላይ ወጣቷ የት እንደገባች አልታወቀም
  • ኤጀንሲው የተጣለበት የፈቃድ እገዳ ተግባራዊ አልሆነም

    ከሁለት ዓመት በፊት አል-ኢስማኤል በተባለ የውጪ አገር የግል ሥራና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ በኩል በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሥራ ኮንትራት ውሏ ፀድቆ ወደ ሳውዲ አረቢያ የተላከችው ወጣት ደብዛ መጥፋት እያወዛገበ ነው፡፡ ወጣቷ ላለፉት 27 ወራት የት እንደገባች የሚያመለክት አንዳችም ፍንጭ አልተገኘም፡፡ ሀያት አሊ መሐመድ በሚል ስም የካቲት 27 ቀን 2005 ዓ.ም ወደ ሳውዲ የተጓዘችው ወጣቷ፤
ከአገር ከወጣችበት ጊዜ ጀምሮ ከቤተሰቦችዋ ጋር አንዳችም ግንኙነት  ባለማድረግዋ ቤተሰቦችዋ የትና በምን ሁኔታ ውስጥ እንዳለች ሊያውቁ እንዳልቻሉ ይገልፃሉ። ወደ ሳውዲ የላካት ኤጀንሲ ሀያት አሊ ያለችበትን ሁኔታና የት እንደምትገኝ እንዲያሳውቃቸው ቤተሰቦቿ ኤጀንሲውን ቢጠይቁም ኤጀንሲው ምላሽ ባለመስጠቱ ለሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ማመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ኤጀንሲው ወጣቷ ያለችበትን ሁኔታ በአፋጣኝ ተከታትሎ እንዲያሳውቅ ያሳስባል፡፡ ኤጀንሲውም ሳውዲ ድረስ ሄዶ ወጣቷን ለማግኘት ቢሞክርም እንዳልተሳካለት ለሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አሳውቋል፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ሀያት አሊ መሐመድ የተባለችው ወጣት በምን ሁኔታና የት እንደምትገኝ ተጣርቶ ምላሽ እንዲሰጠው ለውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ለቆንስላዎች ጉዳይ ክትትልና ድጋፍ ዳይሬክቶሬት ጥያቄ ያቀርባል፡፡
የቆንስላ ጉዳይ ክትትል ቢሮው በበኩሉ፤ ወጣቷ የምትገኝበት ሁኔታ ተጣርቶ እንዲገለፅለት ሪያድ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጥያቄ ቢያቀርብም ከኤምባሲው ምላሽ ሊገኝ ባለመቻሉ የሃያት ቤተሰቦች እጅግ በከፋ ሃዘንና ሰቆቃ ውስጥ እንደሚገኙ  የወጣቷ እህት የኔነሽ አያሌው ለአዲስ አድማስ ገልፃለች፡፡ የወጣቷ ደብዛ መጥፋት በእጅጉ ያሳሰባቸው ቤተሰቦች፤ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጨምሮ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት ሁሉ በተደጋጋሚ የአፋልጉን ጥሪ ቢያቀርቡም እስካሁን ምላሽ አለማግኘታቸውን የጠቆመችው የኔነሽ፤ ኤጀንሲው ተግባሩን በአግባቡ ባለመውጣቱ የሥራ ፈቃዱ እንዲታገድ በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሐምሌ 24 ቀን 2006 ዓ.ም ትዕዛዝ ቢተላለፍበትም ኤጀንሲው አሁንም በስራ ላይ እንደሚገኝ ገልፃለች፡፡ ‹መንግስት ህገ ወጥ ስደትን እቃወማለሁ፤ ዜጎች በህጋዊ መንገድ ወደሚፈልጉበት አገር ለስራ መሄድ ይችላሉ› ባለው መሰረት፣ ዕድሉን ተጠቅማ በህጋዊ መንገድ የሄደችው እህቴ፤ ያለችበት ሳይታወቅ ሁለት ዓመት ከሶስት ወራት ማለፉ እጅግ የሚያሳዝንና ስጋት የሚፈጥር ነው ያለችው የኔነሽ፤
“የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ተረባርበው እህቴ ያለችበትን ሁኔታ እንዲያሳውቁንና ከስጋት እንዲያወጡን እማፀናለሁ” ብላለች፡፡ ስለጉዳዩ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርን ለመጠየቅ ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ ሳይሳካልን ቀርቷል፡፡

Published in ዜና

ሰማያዊ ፓርቲ ከመንግስት የቀረበበትን ውንጀላ ተቃውሟል

      በአሸባሪው ቡድን IsIs ታጣቂዎች አሰቃቂ ግድያ የተገፀመባቸው ኢትዮጵያውያን ሰማዕታትን ለመዘከርና ሽብርተኝነትን ለማውገዝ ባለፈው ረቡዕ መንግስት በጠራው ህዝባዊ ሰልፍ ላይ ተቃዋሚ ከፀጥታ ሃይሎች ጋር የፈጠሩት ግጭት የዓለም አቀፍ ሚዲጠያዎችን ትኩረት ስቧል፡፡በእለቱ በአልጀዚራ በተላለፈ ዘገባ፤ ህዝቡ በከፍተኛ ጩኸትና ቁጣ መንግስትን የሚተቹ መፈክሮችን እያሰማ ባለበት፣ በፀጥታ ሀይሎች የተወሰደው እርምጃ ታይቷል፡፡ ሰልፈኞች ሲደበደቡ የሚያሳዩ የተለያዩ ምስሎችም ተሰራጭቷል፡፡ የኢትዮጵያውያኑን በISIS ታጣቂዎች የመገደል አሰቃቂ ትዕይንት በተደጋጋሚ በምስል አስደግፎ ሲያቀርብ የነበረው ዩሮ ኒውስ፤ ረቡዕ እለት ምሽት ጀምሮ ሰልፉ ሲጀመር የነበረውን ሁኔታና በሰልፉ ማጠናቀቂያ ላይ ፖሊስ ከሰልፈኛው ጋር የተጋጨበትን ትዕይንት አሳይቷል፡፡ በዚህ አጭር የቪዲዮ ትዕይንት፤ መሬት ላይ የወደቁ ወጣት ሴቶች በፖሊስ ሲደበደቡ እንዲሁም አንድን ወጣት በርካታ ፖሊሶች መሬት ላይ በወደቀበት ሲደበድቡ ተስውሏል፡፡ ለረቡዕ እለቱ ሰላማዊ ሰልፍ ትኩረት ሰጥቶ የዘገበው ቢቢሲ በበኩሉ፤ ሰልፈኛው ያሰማውን ተቃውሞና
በመጨረሻም ፖሊስ የሃይል እርምጃ ሲወስድ የሚያሳይ ዘገባ አስተላልፏል፡፡ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን ሰልፉ ከተከናወነ ከሰአታት በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ የታሰበው ሰልፍ በስኬት መጠናቀቁን ጠቁመው አንዳንድ ህገ ወጦች በሰልፉ ላይ ረብሻ ማስነሳታቸውንና ከዚህ ጀርባም የሰማያዊ ፓርቲ እጅ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ረብሻውን ተከትሎ በ7 የፌደራል ፖሊስ አባላት ላይ የመቁሰል አደጋ መድረሱን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ በሰልፉ የተሳተፉ ሰዎች ላይ ጉዳት ስለመድረሱ የተናገሩት ነገር የለም፡፡ በእለቱ ሪፖርተራችን በመስቀል አደባባይ ተገኝቶ እንደተመለከተው፤ በተለይ በቅዱስ ዮሴፍ ት/ቤት አካባቢ በቡድን የተደራጁ ወጣቶች በከፍተኛ ጩኸት መንግስትን የሚያወግዙ መፈክሮች እያሰሙ
ሲቃወሙ እንደነበር ለመታዘብ ተችሏል፡፡ በሰላማዊ ሰልፉ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ ሽብርተኝነትን የሚያወግዘውን ንግግር እያደረጉ ሳለም ከፍተኛ ጩኸትና ተቃውሞ የተስተጋባ ሲሆን አንዳንዶችም ከፖሊስ ጋር ግጭት ፈጥረዋል፡፡ በመንግስት የተጠራውን ሰልፍ ተከትሎ፣ አብዛኞቹ የግልና የመንግስት መስሪያ ቤቶች ዝግ የነበሩ ሲሆን በከተማው አንዳንድ አካባቢዎች የታክሲ እጥረት ተፈጥሮ እንደነበርም ታውቋል፡፡  ፖሊስ ሰልፉን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ የተጠቀመ ሲሆን በርካቶች በግርግርና በትርምስ መሃል ወድቀው ለጉዳት ተዳርገዋል፡፡ የቀይ መስቀል አምቡላንሶችም ተጎጂዎችን ወደ ዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ሲያመላልሱ የነበረ ሲሆን ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው ግለሰቦች ከሰዓት በኋላ እየታከሙ

ከሆስፒታል ወጥተዋል፡፡ ፖሊስ በረብሻው መሃል ያገኛቸውን በርካታ ግለሰቦች በየቦታው በቡድን በቡድን ከሰበሰበ በኋላ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሲያመላልስ እንደነበር የአይን እማኞች ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
መንግስት ተቃውሞውን አደራጅቷል ሲል የወነጀለው ሰማያዊ ፓርቲ፤ ረቡዕ ዕለት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ፣ መንግስት የጠራውን ሰልፍ በመደገፍ አባላቱና ደጋፊዎቹ በሰልፉ ላይ እንዲገኙ ጥሪ ማስተላለፉንና ጥሪውን ተከትሎ እንደማንኛውም ዜጋ በሰልፉ ላይ የሄዱ የፓርቲው አመራሮችና አባላት ገና ወደ መስቀል አደባባይ ከመድረሳቸው በፊት እየታደኑ መታሰራቸውን አስታውቋል፡፡ ፓርቲው “መንግስታዊ ሽብር የህዝብን ቁጣ ያባብሳል እንጂ መፍትሄ አይሆንም” በሚል ባወጣው መግለጫው፤ “መንግስት በዜጎች ላይ የወሰደው የጭካኔ እርምጃ በእጅጉ የሚያሳዝንና በጥብቅ ሊወገዝ የሚገባው ነው” ብሏል፡፡ መንግስት፤ ረብሻውን ያነሳሳው ሰማያዊ ፓርቲ ነው ማለቱን አጥብቆ የተቃወመው ፓርቲው፤ “የመንግስትን ቸልተኝነት በተቃወሙ ሰዎች ላይ የተወሰደው እርምጃ ሳያንስ፣ ጉዳዩን ከአንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር አዛምዶ ተቃውሟቸውን ማጠልሸት በፍፁም ተቀባይነት የሌለው አፀያፊ ተግባር ነው፤ መንግስት ነኝ ከሚል አካል በፍፁም የማይጠበቅ ስህተት ነው” ብሏል፡፡ የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች  የተገኙት እንደማንኛውም ዜጋ በሰልፉ ለመሳተፍ እንደሆነም ፓርቲው አስታውቋል፡፡ በእለቱም 8 ያህል የአመራር አባላቱ ከሰልፉ በፊት እና በኋላ ተደብድበው መታሰራቸውን ፓርቲው አስታውቆ፤ በየፖሊስ ጣቢያውም በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መታሰራቸውን ለማረጋገጥ ችያለሁ ብሏል፡፡ሁለት የፓርቲው እጩ የምርጫ ተወዳዳሪዎችም ፖሊስ ጣቢያ ለታሰሩት የፓርቲው አመራሮች እራት ለማድረስና ለመጠየቅ በሄዱበት ወቅት መታሰራቸውን ፓርቲው አስታውቋል፡፡     


Published in ዜና

     ላለፉት አራት ዓመታት ለንባብ ሊበቃ የቆየው የ“ቆንጆ” መፅሄት ባለቤትና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ካሳ ባለፈው ረቡዕ አገር ጥሎ መሰደዱን ምንጮች አዲስ ለአድማስ ገለፁ፡፡ ጋዜጠኛው በተለያዩ ጊዜያት የመንግስት ደህንነቶች ቢሮው ድረስ በመሄድ ዛቻና ማስፈራራት ስላደረሱበትና ጉዳዩ ከአቅሙ በላይ በመሆኑ አገሩን ጥሎ ለመሰደድ መገደዱን እንደነገራቸው ምንጮቹ ገልፀዋል፡፡ የደህንነት ኃይሎች በየጊዜው ወደ ቢሮው እየሄዱ “ክስና እስር ይጠብቅሃል” እያሉ ያስፈራሩት እንደነበር የገለፁት ምንጮች፤ ፕሬሱን የሚወነጅል ዘጋቢ ፊልም በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እየተሰራ ስለመሆኑ፣ ዘጋቢ ፊልሙ ከሚሰራባቸው የህትመት ውጤቶች አንዱ “ቆንጆ” መጽሄት እንደሆነ መረጃ እንደደረሰውና ደህንነቶቹ በየጊዜው እየተመላለሱ የሚያደርሱበትን ጫና መቋቋም ባለመቻሉ ባለፈው ረቡዕ አገር ጥሎ መሰደዱን ምንጮቹ ጠቅሰዋል፡፡ ከመፅሄቱ ሰራተኞች መካከል አንዱም፤ ደህንነቶች በቅርቡ መጥተው ፍላሽ እና ሌሎች ነገሮችን ቀምተውና አስደንግጠውት መሄዳቸውን ተናግሯል፡፡ ምንም ነገር ቢመጣ ከአገሩ ሳይወጣ በፅናት ለመቆየት እንደሚፈልግ ይነግራቸው እንደነበር የገለፁት ምንጮች፤ በአሁኑ ሰዓት በቀደመው ፅናቱ የሚያስቀጥል ሁኔታ ስላላገኘ አገሩን ጥሎ መሄዱን ነግሮናል ብለዋል፡፡ መፅሄቱ ከተመሰረተ አራት ዓመታት የሞላው ሲሆን የዛሬ ሳምንት ቅዳሜ 100ኛ እትሙ ለንባብ መብቃቱንም ምንጮች ገልፀዋል፡፡ ጋዜጠኛው ላለፉት 13 ዓመታት በጋዜጠኝነት ሙያ ላይ መቆየቱን ለማወቅ ችለናል፡፡  

Published in ዜና

አያዩት ግፍ የለ፤
አይሰሙት ጉድ የለ!
ካራ በዕርግብ አንገት፣ ለዕርድ እየሳለ
“ሠይጣን ሰለጠነ”፣ በደም ተኳኳለ!!!
ሌላነት(Otherness) የሚሉት አዲስ ሾተል አለው
ፀረ-ሰው ለመሆን፣ ማልዶ የሞረደው፡፡
“ዕወቁኝ” ነው የሚል፣ ይህ የገዳይ ቢላ
ሌላም ቋንቋ የለው፣ ወትሮም ለሰው- በላ፡፡
(ይሄን በላዔ-ሰብ፣ ማነው ስሙ? አትበሉ
ስሙን መጥራት ለሱ፣ ነውና እኩይ ድሉ፡፡
ይሄን በላዔ - ሰብ፣ ምን ዓለመ? አትበሉ፡፡
ከጀርባው ያለው ኃይል፣ ያው ደሞ እንዳመሉ
እኔ ነኝ ይለናል፣ ሲሞላለት ውሉ!)
*       *     *
አወይ ያገሬ ልጅ!
ወገኔማ ምን ያርግ፣ አደለም በውዱ
ግድ ሆኖበት እንጂ ነጥፎበት ማዕዱ
ቀን ቢወጣ ብሎ፣ ካገር መሰደዱ፡
ነው እንጂ እንዳቅሙ፣ ጎጆ እስከሚሠራ
የጎሸ ቀን በስሎ፣ ጠሎ እስከሚጠራ
መቼ ጥሞ ያቃል፣ የስደት እንጀራ?!
ወዮ የእናቴ ልጅ! ያ ሁሉ መከራ
ጉሮሮውን ሲያስብ አንገቱን ለካራ!!
*      *     *
ያንድ ቀን አይደለም፣ የጨካኝ ጉድ ጓዙ
ቀበቶን ማጥበቅ ነው፣ የቆራጥ ሰው ደርዙ!
የዚህን ሁሉ ግፍ
የመከራ ምዕራፍ
ገፆቹን ለማጠፍ፤
ራስ በራስ ቆመን፣ ጨክነን በዕርጋታ
ችግሩን ከሥሩ፣ የነቀልን ለታ
ሞት እዬዬ ይላል፣ ሆኖ በ‘ኛ ቦታ!!
ከመቀደም መማር፣ ትልቅ ዋጋ እንዳለው
መቼም ቀን ወደፊት፣ አለመቀደም ነው!!
(በስደት ላይ ሳሉ ልጆቻቸው በአረመኔዎች ለተጨፈጨፉባቸው
ወላጆችና በሐዘን ላይ ላለው የኢትዮጵያ ህዝብ)
                                          (ሚያዚያ 13 ቀን 2007)

Published in ርዕሰ አንቀፅ

መንግሥት፣ ከወዲህ ሲለው ከወዲያ እያፈተለከ አስቸገረው እንጂ አገሪቷን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለማሰለፍ የጀመረውን ጥረት ገፍቶበታል፡፡
አገሪቷ በፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ ስለሆነች የውጭ ኢንቨስተሮች መጥተው በተለያዩ ዘርፎች ቢሰማሩ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ግብዣ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ በጥሪው መሰረት መጥተው በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎችም በርካታ ናቸው፡፡
ከእነዚህ ውስጥ በጨርቃጨርቅ ዘርፍ ተሰማርተው ፋብሪካ ከፍተው ስራ የጀመሩ ኢንዱስትሪዎች ይገኙባቸዋል፡፡ ለእነዚህ ኢንዱስትሪዎች የሚያስፈልገው ዋነኛ የምርት ግብአት (ጥሬ ዕቃ) ጥጥ ነው፡፡ የጥጥ ምርት ደግሞ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አልሳካ እያለ ነው፡፡ በጨርቃጨርቅ ዘርፍ የተሰማሩትን የአገር ውስጥና የውጭ ፋብሪካዎች ችግር ለመፍታት የተዳመጠ ጥጥ ከውጭ ለመግዛት የተደረገው ጥረት ብዙም አልተሳካም፡፡
እንደ ህንድ ካሉ ጥጥ አምራች አገሮች ለመግዛት ቢሞከርም የተፈለገውን ያህል መጠንና የጥራት ደረጃ ማግኘት አልተቻለም፡፡
የአገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬ እንዲሉ… እዚሁ በአገር ውስጥ ገበሬዎች ችግሩን ለመፍታት ባለፈው ዓመት የተጀመረ አንድ ፕሮጀክት ወደ ውጤት እያመራ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የአምናው የተደረገው ጥረት፣ በመተማ ዩኒየን እና በአይካ አዲስ ቴክስታይል መካከል የገበያ ትስስር መፍጠር ነበር፡፡ በስምምነቱ መሰረት፤ መተማ ዩኒየን ለአይካ አዲስ፣ ዘላቂነት ባለው መልኩ 50ሺህ ኩንታል ጥራት ያለው የተዳመጠ ጥጥ እንዲያቀርብ፣ አይካ አዲስም በዓለም አቀፍ ዋጋ እንዲገዛ የገበያ ትስስር ተፈጥሮ ሁለቱም ወገኖች ተጠቃሚ መሆናቸውን የጥጥ አምራቾች ማኅበር ገልጿል፡፡
ፕሮጀክቱ ሲኤምአይኤ የሚባል ሲሆን “በአፍሪካ የተመረተ ጥጥ” የንግድ ስያሜ የእንግሊዝኛ ምህፃረ ቃል መሆኑ ተነግሯል፡፡ ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ በ12 የአፍሪካ አገሮች እየተሰራበት ሲሆን በአነስተኛ አርሶ አደሮች ማሳ የተመረተ ጥጥ ጥራቱን ጠብቆ ዘላቂነት ባለው መልኩ ለፋብሪካዎችና ለተጠቃሚዎች ማቅረብ ነው፡፡ ትስስሩ ውጤታማ ስለሆነ ወደ ሌሎች ዩኒየኖችና የጨረታ ጨርቅ ፋብሪካዎች ለማስፋፋት ለ2007/2008 የምርት ዘመን አራት ዩኒየኖችና የጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች ባለፈው ረቡዕ በኢሊሌ ሆቴል ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
በዚህ ስምምነት መሰረት ከ53 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ያቀፉ ዩኒየኖች 19 ሺህ ቶን የተዳመጠ ጥጥ በማቅረብ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ 10ሺህ አባላት ያሉት ጥረት ወይም መተማ ዩኒየን 3ሺ ቶንስ የተዳመጠ ጥጥ ለአይካ አዲስ ለማቅረብ ተስማምቷል፡፡ በተመሳሳይ 10 ሺህ አባላት የያዘው ዳንሻ አውሮራ ለካኖሪያ አፍሪካ 5ሺህ ቶንስ ያቀርባል፡፡ ባለ 10 ሺህ አባላቱ ሰላም ለኤልሴ 5,500 ቶንስ፣ 13ሺህ አባላት የያዘው ሰቲት ሁመራ ለአልመዳ 5ሺህ ቶንስ፣ ለምለም ወልቃይት ለባህርዳር ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ 3ሺህ ቶንስ ጥጥ ያቀርባሉ፡፡ በአጠቃላይ 53 ሺህ አባላት ያሏቸው አራቱ ዩኒየኖች 21,550 ቶንስ የተዳመጠ ጥጥ በማቅረብ 754 ሚሊዮን 250 ሺህ ብር ያገኛሉ፡፡
ስምምነቱ አነስተኛ የአፍሪካ የጥጥ አምራቾችንና ጥጥ ማዳመጫዎችን የሚያካትት ሲሆን የደላሎችን ጣልቃ ገብነት እንደሚያስቀር ታውቋል፡፡ ሲኤምአይኤ ለጥጥ አምራቾቹ ገበሬዎች የተለያዩ እገዛዎችን ያደርጋል፡፡ የፀረ ተባይ ኬሚካል አያያዝና አጠቃቀም፣ ጥራት ያለው የጥጥ ዘር፣ ውሃ፣ አፈር እንዲጠቀሙ፣ የእንስሳት አያያዝና የደን እንክብካቤ፣ የተፈጥሮ ግብአት አጠቃቀም፣ ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴ እንዲከተሉ ስልጠና ከመስጠቱም በላይ ምርታቸውን በጥሩ ዋጋ እንዲሸጡ ከገዢዎች ጋር ያስተሳስራል፡፡

ሁሉም አገሮች ንጉሣቸው፣ ፕሬዚዳንታቸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትራቸው የሆኑ ቁንጪ አገር መሪ የሚኖርበት ቤተ መንግሥት አላቸው፡፡
ዛሬ 10ሩን የአፍሪካ ምርጥ ቤተ መንግሥቶች እንቃኛለን፡፡


1. ዩኒቲ  ፓላስ፡- (ያውንዴ-ካሜሩን)፡-
በአፍሪካ፣ በቤተመንግሥት ግንባታ ጥበብና ውበት በካሜሩን ዋና ከተማ በያውንዴ የተሰራውን ዩኒቲ ፓላስ የሚስተካከል የለም፡፡
ግድግዳውን የተሸከሙት ረዣዥም ምሰሶዎች፣ የሚያምረው አካባቢ በአረንጓዴ ተክሎችና ሐረጎች ተከቦ ሲታይ የካሜሩን ፕሬዚዳንት የሚኖሩበት ቤተመንግስት የሚገርምና የሚደንቅ የጥበብ ሥራ ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ ሥልጣን ከያዙበት ከኖቬምበር 6,1982 አንስቶ ተንቀባረው የሚኖሩት በዚህ ቤተ-መንግሥት ውስጥ ነው፡፡   

2. አብደን ፓላስ (ካይሮ-ግብፅ)፡-
በተምሳሌታዊ ቅርፆቹና ምልክቶች የተሞላ ነው። የተቀባው ቀለም ውበት የሚመስጥ ሲሆን በዚህ ላይ ክፍሎቹንና ክንፎቹን  ያስዋቡት፣ አብዛኞቹ የእውነተኛ ወርቅ ቅብ ሰዓቶች ፈንጠር ፈንጠር ብለው ተሰቅለዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ ሲታዩ በዓለም ላይ እጅግ ውድ ዋጋ ባላቸው ነገሮች ከተንቆጠቆጡ ቤተ-መንግሥቶች እንደ አንዱ ይቆጠራል፡፡
በካይሮ ከተማ ምስራቃዊ እንብርት፣ ከኳሳር አል-ኒል መንገድ ከፍ ብሎ የተሰራው የአብደን ውበት ከሩቅ የሚስብ ነው፡፡ 500 ክፍሎች ያሉት ይህ የካይሮ ቤተመንግሥት፣ የግብፅ ፕሬዚዳንት ህጋዊ መኖሪያና ዋና ጽ/ቤት ነው፡፡



3. ዩኒየን ቢልዲንግ፡- (ፕሪቶሪያ-ደቡብ አፍሪካ) ይህ ሕንፃ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ህጋዊ መኖሪያና ጽ/ቤት ነው፡፡
የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ ቅርሶች መገኛ በሆነችው ፕሪቶሪያ የተሰራው ይህ ህንፃ ሰፊ የመናፈሻ ስፍራ አለው፡፡
ይህን በእንግሊዝ ቅርፃ ቅርፆች ዲዛይን የሰሩት ሰር ኧርበርት ቤከር የተባሉ የስነ ህንፃ ባለሙያ ሲሆኑ ህንፃውም ከቀላል የኖራ ድንጋይ ነው የሰራው፡፡ ህንፃው፣ 285 ሜትር የጎን ርዝመት ሲኖረው ዲዛይኑ ድንቅ ስለሆነ እዩኝ እዩኝ ይላል፡፡

4. ስቴት ሀውስ ኦፍ ናሚቢያ (ዊንድሆክ - ናሚቢያ) ይህ በ25 ሄክታር መሬት ላይ የሰፈረው የናሚቢያ ሪፐብሊክ መንግሥት መኖሪያ ቤተመንግሥት ሁለት ኪ.ሜ የብረት አጥር፣ ከአናቱ በጥቁር መስተዋት የተከበበና ትልልቅ የጥበቃ ክፍሎች ያሉት ምሽግ ነው፡፡
ይህ ግርማ ሞገስ ያለው ቤተ መንግሥት የናሚቢያ መንግሥት አስተዳደርና የፕሬዚዳንቱ መኖሪያ ነው፡፡፡ የዚህ ቤተ-መንግሥቱ ዲዛይን የተሰራው በደቡብ ኮርያው ኩባንያ Mansude Overseas Project ሲሆን ግንባታው 66 ወራት ነው የፈጀው። የግንባታው ወጪ ውድ እንደሆነና 400 ሚሊዮን የናሚቢያ ዶላር መፍጀቱ ተገልጿል፡፡


5. The Flagstaff House (አክራ - ጋና)
ይህ አስገራሚ ሕንፃ የጋና ፕሬዚዳንታዊ ቤተ-መንግሥት፣ የጋና ፕሬዚዳንት መኖሪያና ጽ/ቤት ነው።
ቤተ መንግሥቱ እንደገና የተገነባውና የተመረቀው በJohn Agyeklum Kufour ዘመነ መንግሥት ሲሆን ለግንባታው ከ45 እስከ 50 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ሲደረግ፣ ተቆጣጣሪው የህንድ ተቋራጭ ነበር።
    

6. ኢቮሎሃ (Iavoloha) ፓላስ፡-
(አንታናናሪቮ - ማዳጋስካር) ይህ አስገራሚ ውበት የተጎናፀፈው ቤተ-መንግሥት የተሰራው በኮረብታ አናት ላይ ነው፡፡ ከማዳጋስካር ዋና ከተማ አንታናናሪቮ በስተደቡብ 15 ኪ.ሜ ርቀር ላይ የተሰራው የማዳጋስካር መንግሥታዊ መቀመጫና የፕሬዚዳንቱ መኖሪያ ነው፡፡

7. ፕሬዚዴንሻል ፓላስ
(ካርቱም - ሱዳን)፡- ዋጋ ሊተመንላቸው በማይችሉ ጥንታዊና, ባህላዊ ቅርፆች የተዋበው የካርቱም - ሱዳን የፕሬዚዳንቱ ቤተመንግሥት የተሰራው ከሙዚየም ቤተ-መንግስት አጠገብ በብሉ ናይል መንገድ ነው፡፡  ታሪካዊ ቤተ - መንግሥት ከመሆኑም በላይ የሱዳን ፕሬዚዳንት መኖሪያና ጽ/ቤት ነው፡፡


8. ፕሬዚዴንሻል ፓላስ
(ኖክቶች - ሞሪታኒያ)፡- የሞሪታኒያ መንግሥት አስተዳደር ዋና ጽ/ቤትና የፕሬዚዳንቱ መኖሪያ ነው፡፡ ቤተ-መንግሥቱ የተሰራው በቻይናውያን ተቋራጮች ነው፡፡

 9.ፕሬዚዴንሻል ፓላስ (ዳካር - ሴኔጋል)፡-
ሰፊ ግቢውና ዓይን የሚስበውና ነጭ ቀለሙ ልዩ ውበት ያጎናፀፈው ቤተ-መንግሥት፣ እጅግ እይታን ከሚማርኩ የአፍሪካ ስፍራዎች አንዱ ነው፡፡
በሴኔጋል ዋና ከተማ ዳካር የሚገኝ ሲሆን የፕሬዚዳንቱ ቤተመንግሥት ነው፡፡


10. ስቴት ሃውስ (ካምፓላ - ዩጋንዳ)፡-
ይህ ቤተ-መንግሥት የዩጋንዳ ፕሬዚዳንት ህጋዊ መኖሪያ ነው፡፡
ከዩጋንዳ ዋና ከተማ ከካምፓላ በስተደቡብ 40ኪ.ሜ ላይ በኢንቴቤ ይገኛል፡፡
ክብረ - በዓላት የሚከበሩበት H ቅርፅ ያለው ሕንፃም አጠገቡ ነው፡፡
የክብረ - በዓላት ማክበሪያው የእንግሊዟ ልዕልት ኤልሳቤጥ ለጋራ ብልፅግና አገሮች የመሪዎች ስብሰባ ዩጋንዳን በጎበኙበት ጊዜ የተስተናገዱበት ነው፡፡ ስቴት ሃውስ ቤተ-መንግሥት፣ በ1.6 ሚሊዮን ዶላር ያህል ወጪ ዋናው መሰረቱን ሳይለቅ እድሳት (ማሻሻያ) ሊደርግለት ነው፡፡  

Page 4 of 17