በየመን በረሃ የአልቃይዳ ድብቅ ካምፕ ውስጥ የነበሩ 55 የቡድኑ መሪዎችና ታጣቂዎች ሰሞኑን መገደላቸውን የዘገበው አሶሼትድ ፕሬስ፣ ጥቃቱ የተፈፀመው በአሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) እንደሆነ ገልጿል፡፡
የአሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ከነባር የስለላ ቅኝት በተጨማሪ የሚሳኤል ጥቃት መፈፀም የጀመሩት በቀድሞው ፕሬዚዳንት ጆርጅ ቡሽ ትዕዛዝ ቢሆንም፤ የአውሮፕላኖቹ ስምሪት እጥፍ ድርብ የተበራከተው በፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ዘመን ነው - በአፍጋኒስታን፣ በኢራቅ፣ በፓኪስታን፣ በየመን፣ በሶማሊያ፣ በሊቢያ ወዘተ፡፡
የሰው አልባ አውሮፕላኖች ስምሪት ለማበርከትም ነው፤ አውሮፕላኖቹን የሚቆጣጠሩ አብራሪዎችም በብዛት እየሰለጠኑ ሲመረቁ የቆዩት፡፡ ዛሬ ወደ 10ሺ ከሚጠጉ የአሜሪካ የጦር አውሮፕላን አብራሪዎች መካከል 5ሺ ያህሎቹ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ለመቆጣጠር የሰለጠኑ ፓይለቶች ናቸው፡፡
አሜሪካ የጦር ካምፕ ውስጥ በኮምፒዩተሮች ቁሳቁሶችና ስክሪኖች ያሸበረቀ ቢሮ ውስጥ በስራ የተጠመዱት የድሮን ፓይለቶች፤ ጌም የሚጫወቱ ነው የሚመስሉት፡፡ ግን የምር ጦርነት ውስጥ ናቸው፡፡ በየመን ሰማይ የስለላ ካሜራዎችንና ሚሳዬሎችን የተሸከመ ሰው አልባ አውሮፕላን አልቃይዳ ካምፕ ላይ ጥቃት እንዲሰነዝር ትዕዛዝ እየሰጡት ነው፡፡
ከአስር ሺ ኪሎ ሜትር ርቀት ሆነው ይዋጋሉ፡፡ ምን አለፋችሁ? የአልቃይዳ ዋና መሪዎችና ወታደራዊ መሪዎች በአብዛኛው የተገደሉት በድሮን ሚሳዬል ነው፡፡ ውጤታማነታቸውን በማየትም፤ የአሜሪካ ኮንግረስ፣ ለውጤታማ ድሮን አብራሪዎች የጦር ሜዳ ኒሻን ለመስጠት የሚያስችል ህግ አዘጋጅቷል፡፡ በአካል የጦር ሜዳን ባይረግጡም፤ ለውጊያ አደጋዎች ባይጋለጡም፤ በውጊያ የጦርነት ድል ሲያስመዘግቡ የጀብድ ኒሻን ሊበረከትላቸው እንደሚገባ ይገልፃል - አዲሱ ህግ፡፡ ግን በዚሁ የሚያበቃ አይመስልም፡፡ የዛሬዎቹ ሰው አልባ የጦር አውሮፕላኖች፣ የርቀት ተቆጣጣሪ ፓይለት ያስፈልጋቸዋል፡፡
አሁን እየተሰሩ የሚገኙ አዳዲስ የጦር አውሮፕላኖች ግን የርቀት ተቆጣጣሪ ፓይለት አያስፈልጋቸውም፡፡ ራሳቸው ችለውታል እኮ! ሃላፊነት እየተቀበሉ የመሰማራትና ወታደራዊ እርምጃ የመውሰድ አቅም አላቸው፡፡ ያኔስ የጀብድ ኒሻንና ወታደራዊ ማዕረግ ለማን ይበረከታል? ለአውሮፕላኖቹ፡፡

Published in ባህል

       ከኢትዮጵያ በእጥፍ የሚበልጥ ሕዝብ የያዘችው ናይጄሪያ በአንድ ምሽት፣ ተዓምረኛ የኢኮኖሚ እድገት አስመዘገበች - 90 በመቶ እድገት። እውነት ነው። ግን፣ “አስመዘገበች” የሚለውን ቃል በቸልታ አትዝለሉት።
ነገሩ ቀላል አይደለም። በፈጣን እድገት እየተንደረደረች መሆኗ የሚነገርላት ኢትዮጵያ፣ አሁን ካለችበት ደረጃ ተነስታ በተዓምረኛ ፍጥነት የ90 በመቶ እድገት እውን ለማድረግ፣ ሰባት አመታት ይፈጅባታል - ከ2500 ቀናት በላይ መሆኑ ነው።
ዎልስትሪት ጆርናል (wsj) እንደዘገበው፤ እስከ መጋቢት 20 ቀን ድረስ፣ በጠቅላላ የኢኮኖሚ ምርት፣ ደቡብ አፍሪካ የአህጉሩ ቀዳሚ ነበረች። የደቡብ አፍሪካ አመታዊ የምርት መጠን 370 ቢሊዮን ዶላር ይገመታል። ከኢትዮጵያ በአስር እጥፍ የሚበልጥ ማለት ነው። በሁለተኛ ደረጃ ላይ ደግሞ ናይጄሪያ ነበረች - በ270 ቢሊዮን ዶላር አመታዊ ምርት።
ይሄ የደረጃ ሰንጠረዥ ከመጋቢት 21 ቀን በኋላ ተቀይሯል። ናይጄሪያ በጠቅላላ አመታዊ ምርት፣ የአፍሪካ ቁንጮ መሆኗን አውጃለች - ለዚያውም በሰፊ ልዩነት። የአገሪቱ አመታዊ ምርት 510 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ ነው የተገለፀው። በሌላ አነጋገር፤ ናይጄሪያ በአንድ ምሽት የ240 ቢሊዮን ዶላር (ወደ ሩብ ትሪሊዮን ዶላር የተጠጋ) እድገት አስመዝግባለች። ኢትዮጵያ በፈጣን እድገት ብትገሰግስ፣ አመታዊ ምርቷ ሩብ ትሪሊዮን ዶላር የሚደርሰው ከ20 ዓመት በኋላ ነው። በናይጄሪያ የአንድ ምሽት ጉዳይ ሆኗል።
ጉደኛውን የናይጄሪያ ዜና የዘገቡ እነ wsj እና ዘ ኢኮኖሚስት የመሳሰሉ የሚዲያ ተቋማት፤ ነገሩ ትንግርት ወይም ምትሃት እንደሚመስል ገልፀዋል። ግን፣ “ሐሰት ነው” ወይም “ስህተት ነው” ብለው አልተቹም። የናይጄሪያ አመታዊ ምርት፣ ከግማሽ ትሪሊዮን በላይ ነው በሚል ተስማምተዋል።
ግን፤ በምንኖርባት ዓለምም ሆነ በሌላ ዓለም፤ “ተዓምር”፣ “ትንግርት”፣ “ምትሃት” የሚባል ነገር የለም። እና ናይጄሪያ በአንድ ምሽት ያስመዘገበችው ወደ ሩብ ትሪሊዮን ዶላር የተጠጋ እድገት፣ “የናይጄሪያ ብሔራዊ ተዓምራት” ውስጥ የማይካተት ከሆነ ምን ተብሎ ሊሰየም ነው? ትክክለኛው ስያሜ፣ “የናይጄሪያ መንግስታዊ ዝርክርክነት” የሚል ነው።
የአንድ አገር አመታዊ ምርት ምን ያህል እንደደረሰ የሚታወቀው፣ ጓዳ ጎድጓዳውን፣ ፋብሪካና ገበያውን፣ የእርሻ ማሳና የከብቶች በረትን ሁሉ እያግበሰበሱ ቆጠራ በማካሄድ አይደለም። በየአመቱ አገር ምድሩን ማሰስ አይቻልም። ታዲያ በመላ አገሪቱ፣ 15 ሚሊዮን የገበሬ ቤተሰቦች ቢኖሩ፤ የሁሉንም አመታዊ ምርት በድምር ለማወቅ ምን መላ አለ? ለምሳሌ፣ ከአንድ ሺ ገበሬዎች መሃል የአንዱ ገበሬ ምርት ላይ በማተኮር ጥናት ማካሄድና በአንድ ሺ ማባዛት ነው መፍትሄው። በዚህ የናሙና ጥናት፣ የ15ሺ ገበሬዎችን የምርት መጠን ላይ መረጃ ይሰባሰባል። ከዚያ፤ ይህ ውጤት በአንድ ሺ ይባዛል - ጠቅላላ የአገሪቱ ገበሬዎች አመታዊ ምርት ለማወቅ። በአንድ ሺ ማባዛት የሚያስፈልገው፤ የአንድ ገበሬ ምርት፣ የአንድ ሺ ገበሬዎችን ምርት ይወክላል ከሚል የጥናት መነሻ ስለተነሳን ነው።
አስር ሺ ትልልቅና ትናንሽ ፋብሪካዎች ቢኖሩ፤ የአንድ ሺ ናሙና ፋብሪካዎችን እንቅስቃሴ በማጥናት በመቶ ማባዛት ይቻላል። የትራንስፖርት፣  የጤና፣ የስልክ፣ የኤሌክትሪክ፣ የባንክ፣ የሸቀጥ አቅርቦት የመሳሰሉ አገልግሎቶችም ላይ ተመሳሳይ የናሙና ጥናት ይካሄድና፤ እንደ ውክልናው ክብደት (weighted mean) በመቶም ይሁን በሺ  እያባዛን ጠቅላላ አመታዊ የአገልግሎት ወይም የምርት መጠን ላይ እንደርሳለን። በሌላ አነጋገር፤ እያንዳንዱ ዘርፍና ንዑስ ዘርፍ፤ እያንዳንዱ አካባቢና መረጃ ... ከላይ እስከ ታች በኢኮኖሚ ውስጥ ምን ያህል ድርሻ እንዳለው በቅጡ ተገንዘበን፣ እንደ የድርሻ ተገቢውን የውክልና ክብደት እስከሰጠነው ድረስ፤ አስተማማኝ ቀመርና ስሌት ይኖረናል ማለት ነው።
በሆነ ምክንያት፣ የውክልናው መጠን ወይም ክብደት ከአመት አመት ቢቀያየርስ? ከጊዜ ወደ ጊዜ ብዙ ነገሮች እንደሚቀየሩ አይካድም። የሕዝብ ብዛትን መጥቀስ ይቻላል። ግን ችግር የለውም። በየአመቱ የሚከሰቱና የተለመዱ ጥቃቅን ለውጦችን ሳንዘነጋ በቀመራችንና በስሌታችን ውስጥ በማስገባት መስመር እናስይዘዋለን። በየአመቱ የገጠር የሕዝብ ብዛት በምን ያህል እንደሚጨምር ይታወቃላ። ግን ባልተለመደ ሁኔታና ፍጥነት፤ ለምሳሌ የአገሪቱ የገበሬዎች ብዛት ወደ አስር ሚሊዮን ቢቀንስ ወይም ወደ ሃያ ሚሊዮን ቢያሻቅብስ? ያኔ ለናሙና ጥናት የምንጠቀምበት ቀመርና ስሌት ላይ ችግር ይፈጠራል። ለምሳሌ፤ ከሃያ አመት በፊት፣ የአበባ እርሻ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ከቁጥር የሚገባ ድርሻ አልነበረውም።
የፊልምና የቪዲዮ ዝግጅትም እንዲሁ። የዛሬውን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ፤ በቀድሞው ቀመርና ስሌት ለመመዘን ስንሞክር፣ የምናገኘው ውጤት የተሳሳተ ይሆናል። የናይጄሪያ መንግስት ሲጠቀምበት የቆየው ቀመርና ስሌትም እንዲሁ፤ ከሃያ አመታት በፊት የነበረውን የኢኮኖሚ መዋቅር ላይ የተመሰረተ ስለሆነ የዛሬውን ሁኔታ በትክክል የማሳየት አቅም አልነበረውም። በናይጄሪያ ባልተለመደ ፍጥነት የተስፋፉት የቴሌኮምና የባንክ አገልግሎት፤ የቴክኖሎጂና የኮንስትራክሽን ቢዝነስ፣ እንዲሁም የፊልምና የቪዲዮ ሥራዎች፤ በኢኮኖሚ ውስጥ ያላቸው ድርሻ እየፈረጠመ መጥቷል። ለሃያ አመታት ያልተለወጠው የመንግስት ቀመርና ስሌት ግን፤ በኢኮኖሚ ውስጥ እየጎሉ ለመጡት ለውጦች ተመጣጣኝ የውክልና ክብደት የሚሰጥ አይደለም። እናም የአገሪቱን አመታዊ ጠቅላላ ምርት በትክክል የማወቅ ወይም የመገመት አቅም አልነበረውም። በየአመቱም የግምቱ ስህተት እየተደራረበ ነው የመጣው። ከሳምንት በፊት የመንግስት ቀመርና ስሌት ተለወጠ። ለሃያ አመታት የተጠራቀመው ስህተትም ተስተካከለ። ይሄ ተዐምር አይደለም። ለበርካታ አመታት የዘለቀ ዝርክርክነት እንጂ።

Published in ባህል

“ካዛኪስታን” የምትባለውን አገር እስከነመፈጠሯ ባታውቋት ችግር የለውም፡፡ የትም ብትሄዱ፣ የካዛኮችን ምድር የሚያውቅ ብዙ አታገኙም፡፡ እንዲያውም፤ ቱሪስቶች ወደ አገራችን ዝር የማይሉት ለምንድነው በማለት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ማማረር ከጀመሩ ውለው አድረዋል፡፡ ለነገሩ እንኳን በአካል ይቅርና ካዛኪስታንን በስም የሚያውቁ ሰዎች ጥቂት ናቸው፡፡ እነዚህ ጥቂት ሰዎችስ እንዴት አወቋት? እንግሊዛዊው ኮሜዲያን “ቦራት”፣ በካዛኪስታን ላይ የሚሳለቅ ፊልም ስለሰራ ነው፡፡
ፊልሙ በመላው አለም መታየት የጀመረ ጊዜ፣ የካዛኪስታን መንግስት የእገዳ መመሪያ አውጥቶ ነበር፡፡ ለምን መሰላችሁ? በካዛኮች ምድር፣ ያለመንግስት ፈቃድ፣ ያለ ባለስልጣን ይሁንታ መጽሐፍ ማሳተምም ሆነ ፊልም መሥራት አይቻልም፡፡ በአገራችን በደርግ ዘመን እንደነበረው፤ በሳንሱር ጽ/ቤት ታይቶና ተመርምሮ፣ ተቆራርጦና ተበርዞ ነው ለፊልምና ለመጽሐፍ ዝግጅት ፈቃድ የሚሰጠው፡፡ ያው፣ ካዛኪስታንም እንደኛው አገር፣ በኮሙኒዝም ውስጥ የነበረች እና በራሺያ ቅኝ ግዛት ስር የቆየች አገር ስለሆነች፣ የሳንሱር አሰራር ገና አልለቀቃቸውም፡፡ አሁንም የመንግስት ስልጣን በአንድ ፓርቲና በአንድ መሪ የተያዘ ነው፡፡ አሁንም ኢኮኖሚው በአብዛኛው በመንግስት ቁጥጥር ስር ነው፡፡ ቱሪስት እና ኢንቨስተር ወደ ካዛኪስታን ዝር የማይለው በዚህ ምክንያት አይደለም እንዴ?!
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት በዚህ አይስማሙም፡፡ አንደኛው ችግር የአገሪቱ የህዝብ ቁጥር 7 ሚሊዮን ብቻ መሆኑ ነው ይላሉ ፕሬዚዳንቱ፡፡ ነገር ግን ሁለት ሚሊዮን ህዝብ ያላት ሞንጐሊያ፣ በርካታ የውጭ ቱሪስቶችንና ኢንቨስተሮችን ለመሳብ ችላለች፡፡ ሞንጐሊያማ ምን ሃሳብ አላት እድለኛ ነች፡፡ የአገር ገጽታን የሚያበላሽ እዳ የለባትም፡፡ ካዛኪስታን ግን እድሏ አልሰምር ብሎ ገጽታዋን ጥላሸት የሚቀቡ ነገረኞችን ተጐራበተች፡፡ ይህ አልበቃ ብሎ ስሟን አሳደፉት፡፡ እነ ማን? እነ ፓኪስታን፣ አፍጋኒስታን ናቸዋ፡፡ ስማቸው ተመሳሳይ ስለሆነ ብቻ፣ ካዛኪስታን የሽብርና የትርምስ አገር ትመስላለች፡፡ ሞንጐሊያ ከዚህ ጥላሸት ነፃ ነች፡፡ ስለዚህ መፍትሔው እንደሞንጐሊያ መሆን ነው፡፡ አፍጋኒስታን ማለት የአፍጋን ቦታ እንደማለት ነው፡፡ ካዛኪስታን ደግሞ የካዛክ ቦታ፡፡ ሞንጐሊያ ማለት የሞንጐል ምድር ስለሆነ፣ የካዛኪስታንን ስም ወደ ካዛኪያ እንቀይረው ብለዋል - ፕሬዚዳንቱ፡፡

Published in ባህል
Saturday, 26 April 2014 12:35

የአይሁዳውያን ፋሲካ

            ክርስቲያኖች “ጌታችንና መድኃኒታችን” ብለው የሚያመልኩት ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በቅዱስ መጽሐፍ እንደተጻፈው ሞትን ድል አድርጎ የተነሳበትን የፋሲካ ክብረ በዓል ከፍ ባለ ስነ-ስርአት ካከበሩት እነሆ ዛሬ ስድስተኛ ቀናቸው ነው፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስን “በጭካኔና በድፍረት፣ ሰቀሉት” እየተባሉ በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ የሚታሙት አይሁዳውያንም ከአውራ ክብረ በአላቶቻቸው አንዱ የሆነውን “ፔሻ” (የማለፍ ቀን) የተሰኘውን በአላቸውን በታላቅ ሀይማኖታዊ ስርአት አክብረው ከጨረሱ የዛሬው የቅዳሜ ሻባት ልክ ስድስት ቀናቸው ነው፡፡
ክርስቲያኖች እንደሚያደርጉት ሁሉ፣ አይሁዳውያንም ይህንን የፔሻ ወይም የማለፍ ቀን ክብረ በአላቸውን ፋሲካ በማለትም ይጠሩታል፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ እጅግ በርካታ ኢትዮጵያውያን ከአይሁዳውያን ጋር ቅርብ የመንፈስና የአካል ቁርኝት ፈጥረው ለሺ ዓመታት የዘለቀውን የታሪካቸውን አብዛኛውን ዘመን ያህል ኖረዋል፡፡ የሆኖ ሆኖ ዛሬ አይሁዳውያን ቢያንስ ከሀያ ሁለት ዓመት በፊት እንደነበሩት ያህል ለኢትዮጵያዊያን በአካል ቅርብ አይደሉም፡፡
ይሁን እንጂ እንግሊዛዊው ይሁዲ ደራሲ ጀምስ በርንስቴይን ሆዌል እንዳለው፤ “መለያየት የልብን ልብ በመኮርኮር የፍቅርን ሳንዱቅ ማስከፈት ይችላል፡፡ እናም የኛም ልብ ትናንት አብረውን ይኖሩ ስለነበሩት አይሁዳውያን ሲል በትዝታ ቢጎተትና “ከቶ እነኛ አይሁዳውያን ወገኖች ይህን ታላቅ በአለ ፋሲካ እንዴት ባለ አኳኋን አክብረውት ይሆን?” ብለን ብናስብና ብንጠይቅ ሀሳባችን መልካም ጥያቄአችንም ተገቢ ነው፡፡
የአይሁዳውያኑ በአለ ፋሲካ የሚከበርበት ቀን፣ የበአሉ ትርጉም፣ የተለያዩ ስያሜዎቹ ባጠቃላይ በአሉ ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅበት ጊዜ ድረስ ያሉት የተለያዩ የአከባበር ስነስርአቶች ዋነኛ መሰረታቸው ከአይሁዳውያኑ ቅዱስ መጽሐፍ ከታናክህ የቶራህ ክፍል ውስጥ ነው፡፡
ቶራህ የአይሁዳውያኑ ቅዱስ መጽሀፍ ከሆነው ከታናክህ ሶስት አበይት ክፍሎች አንዱና የሙሴ መጽሀፍት ተብለው የሚታወቁትን ከኦሪት ዘፍጥረት እስከ ኦሪት ዘዳግም ያሉትን አምስት መጽሀፎች ይዟል፡፡
በቶራህ እንደተገለፀውም አይሁዳውያን የእስራኤል ልጆች በግብጽ ፈርኦኖች እጅ ወድቀው ለአራት መቶ ዓመታት ያህል እጅግ አስከፊ የሆነ የባርነት ህይወት ገፍተዋል፡፡ በዚህ እጅግ መራራ የባርነት ቀንበር ስር ሳሉም “እግዚአብሔር እርሱ አምላካችን ነው፡፡ ሀጢያታችንን ሁሉ ይታገሰናል፣ ይቅርም ይለናል፡፡ ከመከራችንም ሁሉ ያድነናል፣ በማይዝለው ክንዱም ይታደገናል፡፡ አምላካችን እርሱ የእኛም ሆነ የልጅ ልጆቻችንን ልመናም ከቶ ችላ አይልም፡፡” ሰእያሉ ዘወትር አፋቸውን ለምህላ ለሚከፍቱለት አምላካቸው ያቀርቡት የነበረው ልመና በዋናነት ሁለት አይነት ነበሩ፡፡ አምላካቸው እንደተለመደው ሀጢያታቸውን በመታገስ ይቅር ብሎ ከግብጽ ባርነት ነፃ እንዲያወጣቸውና ለቀደመው አባታቸው ለአብርሃም ቃል እንደገባለት ለእነርሱ ትሆን ዘንድ መርጦ ያዘጋጀላቸውን ምድር ይወርሷት ዘንድ ከግብጽ ምድር እንዲያወጣቸው፡፡
እስራኤላዊያን ይሁዲዎች እነዚህን ሁለት ልመናዎች በግብጽ ምድር በባርነት ባሳለፉት ጊዜ ውስጥ ለአፍታም ሳይሰለቹ በማቅረብ አምላካቸውን ተማጽነዋል፡፡ ከአራት መቶ ዓመታት የባርነት ኑሮ በኋላ ግን ኒሳን በተሰኘው ወር፣ ከወሩም በአስራ አምስተኛው ቀን ልመናቸውን በመስማት ከመከራቸው ሁሉ የሚታደጋቸውና ልመናቸውን ሁሉ ከቶም ቢሆን ችላ የማይል አምላካቸው እንደሆነ እንደገና አሳያቸው፡፡
እነሆ፣ ወደር በሌለው በባርነት ጭቆና ይገዛቸው የነበረውን የግብጽን ፈርኦን በታላቅ መቅሰፍት በመምታት፣ የባርነቱን ቀንበር ሰብሮ ነፃ አወጣቸው፡፡ በዚያች ቀንም ለአብርሃም ቃል የገባለትን መሬት ለዘልአለም ርስታቸው አድርገው ይወርሷት ዘንድ አምላካቸው እግዚአብሔር ከግብጽ ምድር በሌሊት አወጣቸው፡፡
በእስራኤል ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ተበታትነው የሚኖሩ አይሁዳውያን ይህን በአለ ፋሲካቸውን ከፍ ባለ ስነስርአት የሚያከብሩትና በአሉም ከአይሁዳውያን አውራ ክብረበአሎች ውስጥ እንደ ዋነኛው ሆኖ የሚቆጠረው፣ ከባርነትና ከመከራ ህይወት ነፃ የወጡበት የነፃነት ቀናቸው በመሆኑ ነው፡፡
እነሆ “ይህም ቀን መታሰቢያ ይሁናችሁ። ለእግዚአብሔር በአል ታደርጉታላችሁ፡፡ ለልጅ ልጃችሁ ስርአት ሆኖ ለዘልአለም ታደርጉታላችሁ።” ተብሎ በቅዱስ ቶራህ እንደተፃፈው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አይሁዳውያን ይህን በአላቸውን ያከብሩታል።
ይህ የአይሁዳውያን በአለ ፋሲካ ከላይ እንደተጠቀሰው፤ ሚያዚያ ስድስት ቀን ተጀምሮ ለአንድ ሳምንት ያህል በተለያዩ ስነ ስርአቶች ሲከበር ቆይቶ፣ ልክ በሰባተኛው ቀን እሁድ ሚያዚያ 12 ቀን በተጀመረበት ድምቀት የበአሉ አከባበር ስነ ስርአት ተጠናቋል፡፡ ከእስራኤል ውጪ እንደ አሜሪካ ባሉ ሀገራት የሚኖሩ አይሁዳውያን ደግሞ አንድ ቀን በመጨመር በአሉን ለስምንት ቀናት ያህል አክብረውታል፡፡
እንግዲህ የበአለ ፋሲካ መነሻው፣ አሰያየሙና ትርጉሙ ከዚህ በላይ የቀረበውን ይመስላል። በመላው ዓለም የሚገኙ አይሁዳውያን ይህንን ታላቅ በአለ ፋሲካቸውን የሚያከብሩት ደግሞ ይህን በመሰለ አኳኋን ነው፡፡
የአይሁዳውያን በአለ ፋሲካ የአከባበር ስነስርአት ዋነኛው እምብርት “ሰደር” በመባል ይታወቃል። ሰደር የሚለው እብራይስጥኛ ቃል ጥሬ ትርጉሙ “ስርአት፣ ቅደም ተከተል” ማለት ሲሆን በበአሉ ወቅት የሚደረገውን የአመጋገብም ሆነ ሌሎች ስነስርአቶች ሁሉ ያጠቃልላል፡፡ በዚህም መሰረት ሀጋዳህ በተባለው የበአለ ፋሲካ የፀሎት መጽሀፍ እንደተዘረዘረው፤ የበአለ ፋሲካ የአከባበር ሰደር አስራ አምስት አይነት ደረጃዎች ወይም ቅደም ተከተሎች አሉት፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ጥቂቶቹ የካዴሽ፣ ኡርሻትዝ፣ ካርፓትዝ፣ ያሼትዝና የማጊድ ስነስርአት ይባላሉ፡፡
ካዴሽ ለበአሉ የቀረበው ወይን ሲጠጣ የሚደረግ የቡራኬ ስነስርአት ሲሆን ኡርሻትዝ ደግሞ ለበአለ ፋሳካ የተዘጋጀውን ምግብ ለመቀደስ የሚደረግ ልዩ የእጅ መታጠብ ስነስርአት ነው፡፡ ካርፓስ በጨው የታሸ ወይም በጨው ውሀ ተነክሮ ከበአሉ ምግብ ጋር የቀረበውን አትክልት የመብላት ስነስርአት ነው። ያሼትዝ ለበአሉ የቀረበውን እርሾ የሌለው ወይም ያልቦካ ቂጣ ሶስቱን መሀል ለመሀል የመቁረስ ስነስርአት ሲሆን ማጊድ ደግሞ አይሁዳውያን የእስራኤል ልጆች፣ ከግብጽ የወጡበትን ታሪክ በቃል የመተረክ ስነስርአት ነው፡
እንግዲህ አይሁዳውያን በአለ ፋሲካቸውን የሚያከብሩት እነዚህንና ሌሎች አስር ስነስርአቶችን በቅደም ተከተል በማከናወን፣ ለበአሉ ተለይቶ የተዘጋጀውን ምግብ በመመገብና ከግብጽ ምድር የወጡበት ድንቅ ታሪክ በመተረክ ነው፡፡
በበአለ ፋሲካ ወቅት ለመላ ቤተሰቡ የሚቀርበው ምግብ የሚዘጋጀው እንደ አዘቦቱ
በበአለ ፋሲካ ወቅት ለመላው ቤተሰብ የሚቀርበው ምግብ በዋናነት ያለ እርሾ ወይም ካልቦካ ሊጥ የተጋገረ ቂጣ፣ ከጠቦት በግ የተዘጋጀ የጎድንና የቅልጥም ጥብስ፣ በጨው የታሸ አትክልትና መራራ ወይም ጎምዛዛ ቅመም ሲሆን ለመጠጥ የሚቀርበው ደግሞ ወይን ነው፡፡
ለበአሉ ተብለው የሚቀርቡት እነዚህ የምግብ አይነቶች የተመረጡት እንዲሁ ሳይሆን የበአሉን ምንነት እንዲያስረዱ ተደርጎ ነው፡፡ ለምሳሌ ካለ እርሾ ወይም ካልቦካ ሊጥ የተጋገረ ቂጣ የሚበላው “እርሾ ያለበትንም ምንም አትብሉ፤ በቤቶቻችሁም ሁሉ ውስጥ ቂጣ እንጀራ ብሉ፡፡” ተብሎ በቅዱስ ቶራህ ስለታዘዘ ነው፡፡ “ሰባት ቀን በቤታችሁ እርሾ አይገኝ፡፡ እርሾ ያለበትንም እንጀራ የሚበላ ነፍስ ከመፃተኛው ጀምሮ እስከ አገር ልጁ ድረስ ከእስራኤል ማህበር ተለይቶ ይጥፋ፡፡” የሚለውን አምላካዊ ትዕዛዝ ለመጠበቅም ማንም አይሁዳዊ ለሰባት ቀን በእርሾ የተጋገረን ቂጣ ወደ አፉ አያዞርም፡፡
የጠቦት በግ ጥብስ የሚቀርበው ጥንታዊውን ለአምላካቸው የሚያቀርቡትን መስዋዕት ለማስታወስ ሲሆን መራራ ወይም ጎምዛዛ ቅመም የሚቀርበው ደግሞ የባርነትን ህይወት አስከፊነት ለማስታወስ ነው፡፡
ለበአሉ የተዘጋጀው ምግብ በዚህ መልክ ተሰናድቶ ከቀረበና የቤተሰቡ አባላት በሙሉ የምግቡን ዙሪያ ክብ ሰርተው ከተቀመጡ በኋላ ስርአቱ በካዴሽ ወይም ለአምላክ ቡራኬ በማቅረብና ለበአሉ የተዘጋጀውን ወይን በመቅመስ ይጀመራል፡፡ የካዴሽ ስነስርአቱ ከተጠናቀቀ በኋላ በቤቱ አባወራ (አንዳንዴ የቤተሰቡ አባላት በመቀባበል ያደርጉታል) የሚቀርብ አይሁዳውያን ከግብፅ ምድር እንዴት እንደወጡ የሚያስረዳ ታሪክ ትረካ ይቀጥላል፡፡
ይህ ትረካ በቤቱ አባወራ የሚቀርበው “እግዚአብሔር እንደተናገረ ወደ ሚሰጣችሁ አገር በገባችሁ ጊዜ ይህን አምልኮ ጠብቁት፡፡ እንዲህም ይሆናል፤ ልጆቻችሁ ይህ አምልኮ ለእናንተ ምንድን ነው? ባሏችሁ ጊዜ እናንተ በግብጽ አገር በእስራኤል ልጆች ቤቶች ላይ አልፎ ግብፃውያንን በመታ ጊዜ ቤቶቻችንን ያዳነ የእግዚአብሔር የማለፍ መስዋዕት ይህች ናት ትሏቸዋላችሁ፡፡” ተብሎ በቅዱስ ቶራህ የተፃፈውን ለመጠበቅ ነው፡፡
በያሻትዝ ስነ ስርአት ጊዜ ካለ እርሾ ከተዘጋጁት ቂጣዎች ውስጥ ወደ ላይ ከፍ በማድረግ፣ መሀል ለመሀል የሚቆረሱት፣ አይሁዳውያን ከግብፅ ምድር በጥድፊያ መውጣታቸውንና ያኔ ምን ያህል ድሆችና ጎስቋሎች እንደነበሩ ለማሳየት ነው፡፡
ለፋሲካ ሰደር የተሰየሙት አይሁዳውያን የቤተሰብ አባላት ለበአሉ ከተሰናዳው ወይን የሚጠጡት አራት ኩባያ ያክል ነው፡፡ ይህም የሆነው እንዲሁ ሳይሆን እያንዳንዱ ኩባያ አምላክ የገባላቸውን ቃል ኪዳን ስለሚወክል ነው። እያንዳንዱ አይሁዳዊ ቤተሰብ ለፋሲካ ሰደር ሲታደም ለመአዱ ከቀረቡት የቤተሰቡ አባላት ቁጥር በተጨማሪ አንድ የወይን መጠጫ ኩባያ ለብቻው ተዘጋጅቶ እንዲቀመጥ ይደረጋል፡፡ ይህ የሚሆነው እያንዳንዱ ቤተሰብ ለዚህ የፋሲካ ሰደር ነብዩ ኤልያስን ስለሚጋብዝ መንፈሱ በቤቱ ውስጥ ካረፈ እንዲቀመጥበት በማለት ነው፡፡
የቂጣ ቆረሳው ስነ ስርአት ከተጠናቀቀና የውዳሴ መዝሙር ከተዘመረ በኋላ፣ ቀጣዩ ስነስርአት ዳግመኛ እጅን በመታጠብ ወይም በራሽትዛህ ስነ ስርአት ይጀመራል፡፡ ቀጥሎም የውዳሴና ሌሎች በዚህ በአል ጊዜ የሚቀርቡ የምስጋና ምግብ በመራራ ወይም በጎምዛዛ ቅመም እያጠቀሱ መብላት ወይም የሹልካን ኦርሽ ስነ ስርአት ይቀጥላል፡፡
እንዲህ እንዲህ እያለ የበአለ ፋሲካ አከባበር ስነ ስርአት እስከ ሰባተኛው ቀን ድረስ ይቀጥላል፡፡ ልክ በሰባተኛው ቀን ኒርዛህ በተሰኘውና በመጨረሻው የአከባበር ስነ ስርአት ሞቅ ባለ የምስጋና መዝሙር ታጅቦ የተለመደውን የበአል ማሳረጊያ “ለከርሞ እየሩሻሌይም እንገናኝ!” በመባባል የበአሉ ፍፃሜ ይበሰራል፡፡
ይህን ጽሁፍ ላነበባችሁ ሁሉ ሂይሂየ ላሽዩም ናይም! ቀኑ መልካም ቀን ይሁንላችሁ!!  

Published in ህብረተሰብ

           የተከበራችሁ አንባቢዎቼ! በቋሪት ተራራ ስለተፈተነው ሙሽራ ከማውሳቴ በፊት ስለቋሪት በጥቂቱ ልንገራችሁ፡፡
ቋሪት በምዕራብ ጎጃም ዞን ከሚገኙ ወረዳዎች አንደኛው ነው፡፡ ወደ ቋሪት ለመዝለቅ ሁለት መንገዶችን መጠቀም ግድ ይላል፡፡ ይኸውም በጂጋ ከተማ በኩል በመኪና ወደ ላይ 45 ኪሎ ሜትር በመጓዝ፣ ወደ ወረዳው ከተማ ገበዘ ማርያም ለመድረስ ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በሞጣ ባሕርዳር መንገድ ከይልማና ዴንሳ ወረዳ ከተማ ከአዴት በመኪና ወይንም በእግር ተጉዞ ወደ ገበዘ ማርያም ለመግባት ይቻላል፡፡ በተለይ ግን ከአዴት እስከ ብር አዳማና ቋሪት ከተማ ወይም ከጅጋ እስከ ገበዘ ማርያም ያለው መንገድ በእጅጉ አስቸጋሪ ነው።
በእነዚያ መንገዶች የሚጓዝ መንገደኛ መኪናው እየነጠረ፣ ወገቡ እየተሰበረ ለመሄድ ይገደዳል። መኪናም እንደ ልብ ስለማይገኝ ነጋዴዎች ሸቀጦቻቸውን ከቦታ ወደ ቦታ የሚያመላልሱትና የሚገበያዩት በአጋሰ5ስ ላይ በመጫን ነው፡፡ በቋሪት አካባቢ ወይበይ፣ ብር አዳማና ጨጎዴ ሐና የተባሉ ቦታዎችን ስም በተደጋጋሚ መስማት የተለመደ ነው፡፡
የቋሪት ከተማ ገበዘ ማርያም በሰንሰለታማ ተራራዎች ሥር ትገኛለች፡፡ ቀደም ሲል ከተማዋ ዳቢ ትባል ነበር፡፡ የቋሪት የመጀመሪያ ገበያ (እናንጊያ ሚካኤል አጠገብ የተመሠረተችው) ፎሲት ገበያ ትባል ነበር፡፡ ከጊዜ በኋላ የፎሲት ገበያ ታጠፈችና በቋሪት ከተማ ዳቢ ላይ ቆመች፡፡ ከተማይቱም እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ ዳቢ ስትባል ቆይታ አሁን ገበዘ ማርያም ተብላ ትጠራለች፡፡
ይህች ውብና ስትራቴጂያዊ ከተማ የተቆረቆረችው በ1955 ዓ.ም ላይ ነው፡፡ በከተማዋ ዙሪያ ዘብ የቆሙ ወታደሮች መስለው ተራራዎች ከብበዋታል፡፡ ከፊት ለፊት ታላቁ የጎምት ተራራ ይገኛል፡፡ ከጎምት ተራራ ቀጥሎ ሹል ተራራ የሚባለው ደረቱን ገልብጦ ቆሟል፡፡ ከሹል ተራራ ቀጥሎ ወስፌ ደንጋይ ተራራ ትገኛለች፡፡ ሌላው ቀስቀስ ተራራ ይሰኛል፡፡ ገበዘ ማርያም ልክ እንደ ዐድዋ የተራራ ሰልፈኛ ወታደር ይበዛባታል፡፡ ረድፉን ተከትሎ አዙሮ አምባ ተራራ፣ ዐመድ በር ታራራ፣ አዳማ ተራራ፣ አብርሃም ተራራ፣ ተራሮቹ በጣም የበዙ ናቸው፡፡
ቦታው ለሰማይ የቀረበ ስለሚመስልና ደጋም ስለሆነ፣ አየሩ በእጅጉ ቀዝቃዛና ነፋሻ ነው፡፡ ጫካ ይበዛዋል፡፡ የደጋ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ልዩ ልዩ ሰብል ይበቅልበታል፡፡ ፈረስ በብዛት ይረባበታል፡፡ ውሀው በጣም ይጣፍጣል፡፡
ከየ ተራሮቹ ሥር ዐራት አፍላጋት ይፈልቃሉ። እነርሱም ወደ ደቡብ አቅጣጫ የሚፈስሰው የብር ወንዝ፣ ወደ ሰሜን የሚወርደው ጡል ወንዝ፣ ወደ ምሥራቅ የሚዘልቀው የሺና ወንዝ፣ ወደ ምዕራብ የሚጓዘው የጀማ ወንዝ ናቸው፡፡ ሺገዝም በአካባቢው ውህጥ /የተዋጠ/ ሆኖ ይፈስሳል፡፡
ነጭ ውሃጎኖ ውሀ ሲዖሎ የተባሉ ወንዞችም በሺና ወንዝ በኩል ወርደው ከየቃ ወንዝ ጋር ይገናኛሉ። የቃም ሞጣ አካባቢ ከሚገኘው ዐቢያ ወንዝ ጋር ይቀላቀላል፡፡ እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት አፍላጋት ኅብር እየሠሩ ከታላቁ ዐባይ ጋር ይቀላቀላሉ፡፡ የዐባይ ወንዝ መፍለቂያ የሆነው ሰከላም ከብር አዳማ በታች 20 ኪ.ሜ ላይ ይገኛል፡፡
በቋሪት ተራራ የተፈተነው ሙሽራ እንደገለጠልኝ፤ ቀደም ሲል በቋሪት ለሀገር ዋስና ጠበቃ፣ የተጣላን አስታራቂ፣ የተከበሩና የታፈሩ፣ የታወቁ የሀገር ሽማግሌዎች ይኖሩ ነበር፡፡ ለአብነት ያህል እነ ጎሹ ገሠሠ፣ እነ ብዙነህ ደስታ፣ አድገህ ንጉሤ(ግራዝማች)፣ ስንሻው ካሣ፣ ይመኔ መነሾና ከልካይ መነሾ፣ ነጋሽ መስፍንና አያልነህ መስፍን (ሁለቱም ግራዝማቾች)፣ ሺፈራው ፈንታ፣ ገላየ፣ አረጋ ተበጀ (ፊታውራሪ) እሸቴ አይቼህ … የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡
ቀደም ሲል በደርግ ዘመነ መንግሥት በቋሪት ሕዝብና በደርግ ባለሥልጣኖች መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ ነበር፡፡ የጠቡ መነሻ አብዮተኛና ፀረ አብዮተኛ የሚል ነው፡፡ ሁለት ተማሪዎች ከጂጋ ከተማ ተነሥተው በእግር ወደ ቋሪት ሲሄዱ በወቅቱ የደምስስ ጦር አዛዥ የጂጋም ወረዳ አስተዳዳሪ የነበረና ስሙን መግለጥ የማልፈልገው ሰው፣ ተማሪዎቹን የኢሕአፓ ወረቀት ልትበትኑ ነው ወደ ቋሪት የምትሄዱት ብሎ በመያዝ ይገድላቸዋል፡፡
የወቅቱን የቋሪት ወረዳ አስተዳዳሪ ቀኛዝማች ውበቴ ደስታንና የፖሊስ አዛዡን 10 ዓለቃ እምሬ ፈንታን ለመያዝ ፈልጎ በአስቸኳይ እንድትመጡ ብሎ ቢልክባቸው እምቢ ይላሉ፡፡ በዚህ ጊዜ “የውበቴንና የእምሬን ጭንቅላት ቆርጬ ባላመጣ እናቴ አልወለደችኝም” ብሎ የደምስስ ጦር አዛዥ ጂጋና ፍኖተ ሰላም እየረገጠ ይፎክራል፡፡ ያስፎክራል። በመኻሉ ደምሳሹ ታጋይ ጦሩን አክቶ ወደ ቋሪት እየመጣ ነው መባልን የሰማው የቋሪት ሕዝብ “ወንድሞቻችንን አሳልፈን እንደ ይሁዳ አንሰጥም” በሚል ቀድሞና ቁልቁል ወርዶ ዝንድብ ከተባለው ቦታ ይጠብቀዋል፡፡
እንደተገናኙ ደምሳሾቹ በአውቶማቲክ መሣሪያ በሕዝቡ ላይ ጥይት ያርከፈክፉበት ጀመር፡፡ ከላይ ከተራራው አክቶ የወረደው የገበሬ ጦር ዝንድብ ላይ ዘመናዊ መሣሪያ ከታጠቀው የደርግ ሠራዊት ጋር ጦርነት ገጥሞ የሚሞተው እየሞተ ግር ብሎ ግፋኑን ወደ ፊት በመሔድ የደምስስን ጦር አዛዥ ይማርከዋል፡፡ ከዚያም የቋሪት የገበሬ ጦር፣ ልብሱን አውልቆ በግራር ዛፍ ላይ ሰቅሎታል፡፡
የደርግ መንግሥትም አባሪ ተባባሪ ናቸው ያላቸውን የቋሪት ጀግኖች አድኖ በመያዝ ረሽኗቸዋል። በወቅቱ በነበረው ሽብር የተነሣ የደብረ ማርቆስ ከተማ ከፍኖተ ሰላም፣ ከጅጋ፣ ከደንበጫ በተፈናቀሉ ስደተኞች ቁጥር ተጥለቅልቃ ነበር። ስለቋሪት ሕዝብ ጀግንነት አስቀድሞ የማውቀው ብዙ ነገር ቢኖርም በሥራ አጋጣሚ ቋሪት በቅርቡ ሄጄ በነበረበት ጊዜ ከጀግንታቸው ባሻገር ዐራት ነገሮችን በፍጥነት ተረዳሁ፡፡ እነርሱም ትሕትናና እንግዳ አክባሪነት፣ ፉከራና ቀረርቶ ወዳድነት፣ የፍቅር ዘፈን ግጥም ደርዳሪነት ናቸው፡፡ ቋሪቶች እንግዳ ተቀባዮች ናቸው የምለውም ያለምክንያት አይደለም፡፡ ገበዘ ማርያም ከተማ እንደገባሁ ምሳ ለመብላት ወደ አንድ ሞቅ ደመቅ ወደ አለ ምግብ ቤት ዘለቅሁና ምሳየን በላሁ፣ ጠጣሁ፡፡ አጠገቤ ቁጭ ብለው ምሳ ሲመገቡ የነበሩ ወጣቶች ጠጉረ ልውጥ መሆኔን ተገንዝበው ከየት ለምን ዓላማ እንደመጣሁ ጠይቀውኝና ተዋውቀውኝ ስንጨዋወት ቆየን። በኋላ ለምግብ ገንዘብ ለመክፈል ስነሣ “ልጆቹ ከፍለውልዎ ሔደዋል” አሉኝ፡፡ በኋላ ስረዳ ልጆቹ የቋሪት ንግድ ባንክ ሠራተኞች እንደሆኑ አወቅሁ። ማታ ደግሞ በአጋጣሚ ከወረዳው ቤተክህነት አስተዳዳሪና ሠራተኞች ጋር መተዋወቄን ምክንያት አድርገው ራት ጋብዘው፣ ለአልጋም ከፍለውልኝ እንደሄዱ ተነገረኝ። በየ ሱቁ በሄድኩበት ሁሉ መስተንግዷቸው ይማርካል፡፡
በትራንስፖርት ረገድ በአካባቢው ትልቁ ችግር መኪና ነው፡፡ የወረዳው ፖሊስ ጽ/ቤት መኪና መድቦልኝ ብር አዳማ ንኡስ ከተማ ድረስ ጋቢና በክብር አስቀምጦ ልዩ መስተንግዶ አድርጎልኛል። ከዚህም የተነሣ ለሁልጊዜም የሕዝቡ እንግዳ አክባሪነት፣ ፍቅሩና ትሕትናው ከልቤ ውስጥ ይኖራል፡፡
ቋሪት ጎበዘ ማርያም ከተማ ሲያስተጋቡ ስለሰማኋቸው የፉከራ የሽለላ፣ የዘፈን/የፍቅር ግጥሞች በጥቂቱ ለአንባቢዎቼ  ለማስገንዘብ ከቀረርቶዎቹ እጀምራለሁ፡፡
“ቤቴ በረሀ ነው ጫካ ነው አገሬ፣
ማን ደጄን ረግጦት መቼ ተናግሬ፡፡
ቀን ያወጣል ብለው የዘሩት በቆሎ፡፡
ፍሬ ሳይሰጥ ቀረ ያለጊዜው በቅሎ፡፡
ገና ሳይታወቅ ክፉ ይሁን በጎ፡፡
እንዴት ሰው ይቆርጣል አንድ አንጀት ፈልጎ፡፡
ቡሬ አለ ጠመንጃ ሰከላ አለ ጥይት፡፡
ከተኮሰ አይስትም አነጣጥሮ ቋሪት፡፡
አትንኩኝ ማለቱ የእናት ያባቱ ነው፡፡
ምን ይገኝበታል ደሞ የቋሪት ሰው፡፡”
ስለጎጃም ጀግኖች የሚከተሉት ዘፈኖች ይዘፈናሉ፡፡
“የተወለድኩብህ ቋሪት ደጋ ዳሞት፣
አርገኝ እንደበላይ ሰው ፈርቼ እንዳልሞት፡፡
አባቴ የሰጠኝ ሱሪ ከሚቀደድ፣
መታነቅ ይሻላል መሰቀል በገመድ፡፡
ስለቴ ቢሰምር ነግሬያለሁ ለዐባይ፣
ከማይሞቀው ኑሮ አርገኝ እንደ በላይ፡፡
ሺፈራውም ሞተ እጅጉም ቆሰለ፡፡
የበላይ በልጅጉ መሬት ወርዶ ዋለ፡፡
እምቢ አለ ጠመንጃው አልተኩስም አለ፡፡
በላይ በዐደባባይ ስለተሰቀለ፡፡”
“የጎጃምን ሱሪ ሰፊ አበላሽቶበት፣
መንገደኛው ሁሉ ጉልበቱን አየበት
ቋሪትንና ብር አዳማን የሚያናውጡ የፍቅር ግጥሞችም አሉ፡፡ ለአብነት ያህል ጥቂቶቹ ተጠቅሰዋል፡፡
 “አዳማ ላይ ሆኘ ባስጠራሽ አቦላ፣
ዐባይ ከጠበሉ ሄድሽ አሉኝ ሰከላ፡፡
መቼ ትመጫለሽ መቼ ልጠብቅሽ፣
ዋሸራ ወጥቼ ቅኔ እንድዘርፍልሽ፡፡
ጎንጅነሽ ቆለላ ዋሸራ ማርያም፣
ወርደሽ እንገናኝ ኢየሱስ ገዳም፡፡
ነይ ከደጋ ዳሞት፣
ናፍቄሽ እንዳልሞት፡፡
ጨካኝ ናት እያሉ ሲሉ ሰማኋቸው፡፡
ካልነኳት አትነካም ብየ ነገርኳቸው፡፡
እንዲህ ብለሽ ብለሽ የመጣሽ እንደሆን፣
አገሩ ይሰብሰብ አልችልም ብቻየን፡፡
ድረሽ በማለዳ፣
ድረሽ ከብት ስንነዳ፡፡
ድረሽ በማለዳ ድረሽ፣
ከብቶቹን ይዘሽ፡፡
ድረሽ በማለዳ፣
የፍቅር እንግዳ፡፡
እጠብቅሻለሁ ቤቴን አሳምሬ፣
ሌሊቱ ሲነጋ ድረሽልኝ ፍቅሬ፣
እኔ አልተመቸኝም ጅጋ ነው አዳሬ፡፡
ከብት አሰማርቼ ከላይ ከተራራው፣
ከታች ሆነሽ ጥሪኝ ብቅ ብለሽ ከማማው፡፡
ያው ደበሎ ለባሽ እረኛ ነኝና፣
እጠብቅሻለሁ ደርሰሽ ጥሪኝና፡፡
ወይ ወርጀ ልምጣ ከብቶቹን ለቅቄ፣
አላማረብኝም ከወዳጅ ርቄ፡፡
ከማታው ወድጀ አንቺን ስል፣ አንቺን ስል፣
አስፈጀሁ የሰው እህል፡፡
ትመጫለሽ ብየ ሳይ ማዶ ሳይ ማዶ፣
ዓይኔ ሆነ ባዶ፡፡
እንዲያው ከፈረሱ ከለመድሺው በቅሎ፣
ወንድ እንዳይስቅብኝ በእኔ ግዳይ ጥሎ፡፡
እመጣለሁ ብለሽ ነግረሽኝ ነበረ፣
እናስ ምነው ጠፋሽ ቤቴ ክፍት አደረ፡፡
አንቺ የንጋት ወፍ የማለዳ እንግዳ፣
መቼ ብቅ ትያለሽ ባንቺ እኔ ስጎዳ፡፡
ቀኑ አልተመቸኝም ዐርባ ነው ሌሊቱ፣
እንቅልፍ ያልወሰደኝ ጥሎብኝ ነው ብርቱ፡፡
በዳር እንዳዋልሺው እንደመቀነትሽ፣
ጣል አርገሽ ነጠላ አርጊኝ በወገብሽ፡፡
ገና በልጅነት ስትግደረደሪ፣
መብላት ያለብሽን ሳትበይ እንዳታድሪ፡፡”
ልጃገረዶች ደግሞ ቆንጆዎች፣ ረጃጅሞችና ወገበ ቀጭኖች ናቸው፡፡
ባለትዳር ያልሆነ ሰው በቀላሉ በቋሪት ልጃገረዶች የአነጋገር ለዛ፣ ፈገግታና ውበት ተማርኮ እዚው የመቅረት ዕድሉ የሰፋ ነው፡፡ ደግነቱ እኔ ባለትዳር መሆኔ ጠቀመኝ፡፡
በቋሪት ተራራ የተፈተነው ሙሽራም ከምሥራቁ የጎጃም ክፍል ወደ እኛው ምዕራብ ጎጃም ዞን መጥቶ ቋሪት የቀረው በአንዲቱ ወጣት ውበት ተማርኮና በፍቅርዋ ተነድፎ ነው፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በፊት የፍ/ቤት ጸሐፊ፣ በኋላ ዳኛ የነበረው አቶ ዋልታንጉሥ ጥበቡ ይባላል፡፡ ተፈቃሪዋ ደግሞ የያኔዋ ወጣት ጦቢያው አበሻ ትባላለች፡፡ በአቶ ዋልታንጉሥ ልብ ውስጥ ሁነኛ ስፍራ ስለአገኘች አቶ ዋልታንጉሥ ሽማግሌ ልኮ ቀን ቆርጦ ያገባታል፡፡
ጋብቻውን ምክንያት በማድረግም በሹል ደንጋይ አናት ላይ የምትኖረው የሙሽራዋ ታላቅ እህት ሙሽሮችን መልስ ይጠራሉ፡፡ ሙሽሮቹ ሚዜዎቻቸውን አስከትለው እስከ ተራራው ጥግ ድረስ በመከራ ይጓዛሉ፡፡
ከዚያ ሌሎች እንደምንም በደረት እየተሳቡ ከተራራው ሹል ድንጋይ አናት ላይ ሲደርሱ የያኔው የፍርድ ቤቱ ጸሐፊ ሙሽራው ዋልታ ከመንገድ ወደ ከተማው ይመለሳል፡፡ ሚዜዎቹ ሙሽራዋን ይዘው ወደ ድግሱ ቤት ሲያመሩ፣ የሙሽራዋ ታላቅ እህት ሙሽራውስ? ይላሉ፡፡
“ተራራውን ለመውጣት ስለአልቻለ ከመንገድ ተመልሷል” ይሏቿል፡፡ በዚህ ጊዜ የሙሽራዋ እህት “ሙሽራው ዳኛ በወሰካም ቢሆን ካልመጣ በምንም ታምር የጠላው ጋን አይከፈትም፣ የመሶቡ እንጀራም አይቀርብም” ይሏቸዋል፡፡
ከዚያ የፍርድ ቤቱ ጸሐፊ እስከ ተራራው ጥግ ድረስ በበቅሎ ከሄደ በኋላ፣ በጠንካራ ጎረምሶች በወሳንሳ (በቃሬዛ) ተይዞና ወደ ተራራው አናት ወጥቶ የመልሱን ድግስ ከበላ በኋላ፣ በወሰካ ተኝቶ ተራራውን ከወረደ በኋላ ወደ ቋሪት ገበዘ ማርያም ተመልሷል፡፡
የያኔዎቹ ሙሽሮች፣ የዛሬዎቹ ባለትዳሮች ማንነት በፎቶግራፍ በተደገፈ መረጃ ስለቀረበ ለማየት ይቻላል፡፡

Published in ህብረተሰብ

በዕቁብ ስም የሚሰበስቡት ገንዘብ ደመወዝ ነው የበረሃ አበል?

ይህ ዕድሜው ከ14 ዓመት የማይበልጥ ልዩ የትምህርት ፍቅርና አቅም ያለው ሕፃን የሥራ ቦታ ነው - መስቀል አደባባይ፡፡ ከትምህርቱ ሰዓቱ ውጪ ባለው ጊዜ ከጫማ ማሳመር ሥራ የሚያገኛትን ገቢ እንደወትሮው ለ’ራሱና ለአቅመ ደካማ እናቱ አንጀት መለጎሚያ እንዳትውል የሚያደርጋት ክስተት ተፈጠረ፡፡ አንድ ሚኒባስ ተሳፋሪዎችን ጭኖ ከጊዮን ሆቴል ወደ መስቀል አደባባይ ይነጉዳል፡፡ ለሌሎች አሽከርካሪዎች ቅድሚያ እንዲሰጥ የሚያስገድደውን የትራፊክ ምልክት ጥሶ ተፈተለከ፡፡ ከለጋሃር ወደ መስቀል አደባባይ የሚጓዝ የከተማ አውቶብስ አለአግባብ ወደ መስመሩ የገባበትን ይህንን ሞገደኛ ሚኒባስ ላለመግጨት መሪውን ጠቅልሎ ወደ አደባባዩ ጥግ (አሁን ታክሲዎች ወደሚቆሙበት ቦታ) በጭንቀት አመራ፡፡ ጥቂት የማይባሉ ላዳ ታክሲዎችን ገጭቶ 70 ሜትር ድረስ ተንሸራቶ ኤግዚቢሽን ማዕከል መግቢያ ደረጃ ጋ ሲደርስ ቆመ።
ከዚህ ሁሉ አደጋ መካከል ተዓምር በሚባል ሁኔታ ሚኒባሱና አውቶብሱ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ቀላል እና መካከለኛ ጉዳት ብቻ ደረሰባቸው፡፡ ከመንገድ ውጪ የሥራ ቦታው ላይ የነበረው ሕፃን ግን በአውቶብሱ ጎማ ተዳምጦ ብርኩ ደቀቀ - የአልጋ ቁረኛም ሆነ፡፡ በሰሙት ነገር ልባቸው የደማው የሕፃኑ ደንበኞች፤ የሚኖርበትን ቤት አፈላልገው ለሕክምና እና ለመቋቋሚያው ይሆነው ዘንድ ለሕፃኑ ካሳና ድጋፍ ለማግኘት ጥረት ያደርጉ እንደነበር አውቃለሁ፡፡ ለደረሰበት አደጋ ምንም አስተዋፅዖ የሌለው ታዳጊ አጭር ታሪክ እዚህ ላይ ተቋጨ፡፡
አንድ ወጣት የታክሲ ሹፌር የመኪናውን ማርሽ ወደኋላ አስገብቶ ብዙ ተሳፋሪና ታክሲ ከሚበዛበት የታክሲ መጫኛና ማውረጃ ሥፍራ በጥድፊያ ለመውጣት ሲሞክር ታክሲ በመጠበቅ ላይ የነበረች ወጣትን በመኪናው ገፍትሮ በመጣሉ ክስ ቀርቦበት ምርመራ ተጀመረ፡፡ በወጣቷ ላይ ምንም አካላዊ ጉዳት አለመድረሱ በሕክምና ማስረጃ በመረጋገጡ በከሳሽና ተከሳሽ መካከል በተደረገ ዕርቅ እልባት አገኘ፡፡ ሹፌሩም ከስህተቱ እና ካየው ውጣ ውረድ በመማሩ፣ ዳግም ያለጥንቃቄ (በእሱ አገላለፅ ያለወከባ) እንደሚነዳ ተገዝቶ ወደ ስራው ተመለሰ፡፡
ከዚህ አደጋ ሁለት ሳምንት በኋላ ወጣቷን ከገጨበት ቦታ በጥቂት መቶ ሜትሮች ርቀት ላይ ተሳፋሪ ጭኖ የሚበርበትን መስቀለኛ መንገድ በማቋረጥ ላይ የነበረ የ18 ዓመት ወጣትን በመኪናው ገጭቶ፣ የእግረኛ ማቋረጫ መስመሩ ላይ ዘረረው፡፡ ሹፌሩ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ‘ራሱን የሳተው ወጣት ወደ ሆስፒታል ተወሰዱ፡፡ ከገባበት ሰመመን ነቅቶ የደረሰበትን ጉዳት ለማወቅ አድል ያላገኘው ወጣት ከጥቂት ቀናት በኋላ በሆስፒታል አልጋ ውስጥ ሳለ ሕይወቱ አለፈች፡፡ ሹፌሩ የቀረበበትን በቸልተኝነት የሰው መግደል ወንጀል ክስ ሲከታተል ቆይቶ ለፍርድ መቀጠሩን አስታውሳለሁ፡፡ ቀድሞ ካደረሰው አደጋ አንዳችም ትምህርት ያልወሰደ፣ ፍፁም ኃላፊነት የማይሰማው ሹፌር አጭር ታሪክ እዚህ ላይ ተቋጨ።
አንጋፋው አየር መንገዳችን ካፈራቸው ምርጥ ወጣት አብራሪዎች አንዱ የሆነው ካፒቴን ትምህርቱን አጠናቆ በበረራ ሥራ የተሰማራ ቢሆንም እናት አገሩ ዕውቀቱን እና ትጋቱን ለመጠቀም፣ ወላጆቹም የልጃቸውን ስኬት ለማጣጣም እምብዛም አልታደሉም፡፡ ከሥራ መልስ ምሽቱን ሲዝናና አምሽቶ፣ ተሽከርካሪውን እየነዳ ወደቤት በመመለስ ላይ ሳለ ዋናውን መንገድ ስቶ ለግንባታ በተገለበጠ ጠጠር አልያም አሸዋ ላይ በመውጣቱ መኪናው ተገለበጠ፡፡ ክቡር ሕይወቱም በአደጋው ምክንያት አለፈች፡፡ መኪና ከማሽከርከሩ በፊት ሊወሰዱ የሚገባቸውን ጥንቃቄዎች ባለማከናወኑ፣ ሕይወቱን በማጣቱ በቤተሰቦቹ ላይ የሐዘን ከል የወረደ ወጣት አጭር ታሪክ በዚህ ተቋጨ፡፡
 እነዚህን እና መሰል የትራፊክ አደጋ ዜናዎችን መመልከት፣ ማዳመጥ፣ ማንበብ ወዘተ ከደማችን ጋር የተዋሀደ ይመስለኛል፡፡ ለዚህም አንዱ ማረጋገጫ ከዓመታት በፊት ኮልፌ አካባቢ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የደረሰው ዘግናኝ እልቂትም ሆነ በቅርቡ ዘነበ ወርቅ አካባቢ ገደል ውስጥ ተገልብጦ ከፍተኛ አደጋ ያስከተለው የአንበሳ የከተማ አውቶብስ አደጋ የደረሱት በሰለጠኑ አገራት ቢሆን ብሔራዊ ወይም ከተማ ዓቀፍ የሃዘን ቀን ሊያሳውጁ የሚችሉ መሆናቸው ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
የትራፊክ አደጋ እያስከተለ ያለውን ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳትና ክስረት፣ ዕንባና ሳግ እየተናነቃቸው ለረዥም ዓመታት ሲገልፁልን በነበሩት ነፍስ-ሄር ሳጅን ዳንኤል እግር የተተኩት ረዳት ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ የአደጋው መበራከት፣ አሰቃቂነቱ እና አሁንም ድረስ ከአሽከርካሪዎችም ሆነ ከእግረኞች የሚፈለገው ለውጥ በሚፈለገው መጠን አለመምጣቱ እያስቆጫቸው በተመሳሳይ ስሜት ዘወትር ተለወጡ ይሉናል፡፡ ለዚህም ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል፡፡
በአገር አቀፍም ሆነ በክልል ደረጃ በሚሰራጩ የቴሌቪዥንና የሬዲዮ የመንገድ ደህንነት ዘጋባዎች የትራፊክ አደጋ መንስዔዎች ናቸው ተብለው በአብዛኛውን የሚጠቀሱ ነጥቦች አሉ - የአሽከርካሪ ጥፋት፣ የተሽከርካሪ የቴክኒክ ብቃት ማነስ፣ የእግረኛ የጥንቃቄ ጉድለት እና ከመንገድ ጋር የተያያዙ ችግሮች፡፡ ከዚህ ሁሉ ጎልቶ የሚታየው የአሽከርካሪ ጥፋት ነው፡፡ የዛሬው ፅሑፌ ርዕሰ ጉዳይም አይነኬ ከሆኑት ጉዳዬች አንዱ ስለሆነው ነው - እየገደሉን ስላሉ አንዳንድ የትራፊክ ፖሊሶች ጎጂ ድርጊቶች፡፡
3ኛው የትራፊክ አደጋ ሳምንት ከሚያዚያ 06 ቀን ጀምሮ በተለያዩ መርሐ-ግብሮች እየተከበረ ከመሆኑ አንፃር፣ ይህንን አይነኬ ሃሳብ በማንሳት፣ የትራፊክ አደጋን ዘርፈ ብዙ ጉዳቶች ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ በማሰቤ የግል ምልከታዬን እነሆ፡፡

ማሳያ አንድ - ትርፍ ሰው መጫን
አንድ ተሽከርካሪ ከመጫን አቅሙ በላይ ሠው ወይም ዕቃ ከጫነ እንደ ፍሬን እና ጎማ ያሉ የተሽከርካሪው አካላት ሥራቸውን በአግባቡ ማከናወን ስለማይችሉ፣ ተሸከርካሪው ለአደጋ የመጋለጥ እንድሉ ከፍተኛ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልፃሉ፡፡ ለዚህ ችግር ተጋላጭ ከሆኑት ተሽከርካሪዎች ውስጥ የህዝብ ማመላለሻ ሚኒባሶችና ሌሎች የህዝብ ማጓጓዣ ተሽከርካሪዎች ግንባር ቀደሞቹ እንደሆኑ ሲገለፅ በተደጋጋሚ እንሰማለን፡፡
የህዝብ ማመላለሻዎች ትርፍ የሚጭኑበት ዋነኛ ምክንያት ብዙ ሰው በመጫን የገንዘብ ጥቅማቸውን ከፍ ማድረግ እንደሆነ መገመት ባይከብድም ከሐዋሳ አዲስ አበባ፣ ከአዲስ አበባ በዝዋይ በኩል ቡታጅራ፣ ከባሕርዳር አዲስ አበባ፣ ከሻሸመኔ ሶዶ፣ ከመቀሌ አክሱም፣ ከአዳማ አዋሽ አርባ ባደረግኳቸው ጉዞዎች ስለጉዳዩ የጠይቅኳቸው ሹፌሮች የሠጡኝ መልስ  ትርፍ የሚጭኑበት ሌላም ምክንያት እንዳላቸው ያስገነዝባል፡፡ ብዙዎቹን የሚያስማማው መልስ የመጀመሪያው ሲሆን አጠቃላይ ሐሳባቸው በግርድፉ የሚከተለውን ይመስላል፡፡
ምክንያት አንድ፡- ለምሳሌ አንድ ሹፌር በሰው 25.00 ብር በሚከፈልበት መስመር አራት ትርፍ ተሳፋሪ ቢጭን 100.00 ብር ያገኛል፡፡ ከዚህ ብር የተወሰነውን ለሚያስቆመው ትራፊክ ቢያካፍል ቀሪዋን ለኪሱ ከማድረጉ ባሻገር፣ በዛው ቀን ትርፍ ጭኖ ሲሄድ እንዳይቀጣ ከትራፊኩ ጋር “ደንበኝነትን” መመስረቻ ስለሚሆነው የቀን ገቢውን ከፍ ያደርገዋል፡፡
ምክንያት ሁለት፡- አንድ ሹፌር በሚሰራበት መስመር በሚገኙ ሆቴሎች፣ ግሮሰሪዎች ወይም ሱቆች ውስጥ ዕቁብ ጥሎ ስሙን ካስመዘገበ፣ በዛ መስመር የሚገኙ የዕቁቡ አደራጅ ትራፊኮች ትርፍ ቢጭንም ታርጋውን ከሩቅ በማየት ብቻ ሳይቀጡ ያሳልፉታል፡፡ ብቻ ከሱ የሚጠበቀው ዕቁቡን ሳያቋርጥ መጣል ነው፡፡
ዕቁብ በሹፌሮቹ ቋንቋ “አንዳንድ” የትራፊክ ፖሊሶች በቡድን እና በግል ተደራጅተው በዕቁብ ስም በወኪሎቻቸው አማካኝነት የሚሰበስቡት ግብር መሆኑ ነው፡፡
ምክንያት ሶስት፡- በዚህ መስመር የሚሰራ ሹፌር “ዕቁብ” የማይጥል ወይም በሹፌሮቹ ቋንቋ “የማይገባላቸው” “የማይወርድላቸው” ከሆነ የዕቁቡ አደራጅ “ትራፊኮች” እየተቀባበሉ በረሃ መሐል አለአግባብ የመኪናህን ጥሩንባ በተከለከለ ቦታ ነፋህ ወይም በጠራራ ክረምት ዝናብ መጥረጊያህ አይሰራም ብለው የክስ ወረቀት ይሰጡታል፡፡ አልያም ትክክለኛ ስለመሆኑ አንዳችም የሚያጠራጥር ነገር የሌለበትን መንጃ ፍቃድ ሐሰተኛ ሳይሆን አይቀርም በማለት ወደ ፖሊስ ጣቢያ ይወስዱታል፡፡ ስለዚህ ምርጫው ሁለት ነው ፤ “ዕቁብ መጣል” ወይም ስራውን ማቆም፡፡
ሥራውን ማቆም ስለማይታሰብ “ዕቁብ ይጥላል”፡፡ ዕቁብ ከጣለ ደግሞ አሁንም በሹፌሮቹ ቋንቋ “ዘጭ አድርጎ” (ብዙ ትርፍ ተሳፋሪ ጭኖ) ይጓዛል፡፡
ምክንያት አራት፡- አስተውላችሁ ከሆነ ትራፊክ አስቁሞ መንጃ ፍቃድ ሲጠይቃቸው የመኪናውን የባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተር (ሊብሬ) ብቻ እየመዠረጡ በልበ ሙሉነት አሳይተው መንገዳቸውን ያለክስ የሚያልፉ አንዳንድ ሹፌሮች አሉ፡፡ መሰል ሹፌሮችን “የባሉካ ሹፌር”፣ “የሳጅን ሹፌር” ወይም “እርገጥ” ይሏቸዋል፡፡ እርገጥ የሚሏቸው ያለ ጭንቀት ነዳጃቸውን ጥግ ድረስ እየረገጡ መንገዱ ስለሚጓዙ ነው፡፡ ሊብሬ የሚያሳዩት የተሽከርካሪው ባለቤት በዛ ወይም በአቅራቢያ መስመር ትራፊክ ፖሊስ፣ የትራፊክ ፖሊስ የቅርብ ቤተሰብ ወይም የመንገድ ትራንስፖርት ተቆጣጣሪ፣ ሥምሪት ኃላፊ ወይም የቅርብ ቤተሰቡ መሆኑን ለማሳወቅ ነው፡፡ እነዚህ ክስ የማይነካቸው (Charge Proof) ተሽከርካሪዎች ናቸው - ዘጭ አድርገው ሰው የሚጭኑ፡፡      
መደምደሚያ አንድ
ከላይ ያየናቸው እና በቦታ ውስንነት ያልገለፅኳቸው ሌሎች ምክንያቶች ሲጠቃለሉ፣ ሙሰኛ ትራፊክ ፖሊሶች በመኖራቸው ምክንያት ሹፌሮች ትርፍ ሰው ለመጫን ይደፋፈራሉ፣ ይበረታታሉ ወይም ይገፋፋሉ የሚል መደምደሚያ ላይ ያደርሱናል፡፡ ትርፍ መጫናቸው ደግሞ የተሽከርካሪውን ለአደጋ የመጋለጥ ዕድል ከፍ ማድረጉ አይቀሬ ነው፡፡

Published in ህብረተሰብ

ፓርላማው እንዲሟሟቅ ትኩስ ቡናና ሳቅ ያስፈልጋል!

        ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ለፓርላማ ያቀረቡት በፋሲካ ማግስት ነው ማለት ይቻላል- ባለፈው ሐሙስ፡፡ ለዚህም ነው አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት ከሌላው ጊዜ በተለየ እንቅልፍ እንቅልፍ ያላቸው (የበዓል ማግስት እኮ ይጫጫናል!) ለነገሩ … ያንን ሁሉ ሰዓት አዳራሽ ውስጥ መሰብሰብም እኮ እንቅልፍ ያመጣል፡፡ ምናልባት በጣም የባሰበት እኮ ጥያቄውን ለጠ/ሚኒስትሩ ከአቀረበ በኋላ፣ “ለሽ” ሊል ይችላል፡፡ ደግነቱ እኛ እንሰማዋለን (“እኛ” ወካዮቼ ማለቴ ነው!) በነገራችሁ ላይ በበቀደሙ ፓርላማ  እንቅልፍ ያስቸገራቸውን የምክር ቤት አባላት ለመውቀስ አይደለም - የሚመለከተው አካል መፍትሄ እንዲያፈላልግ መተንኮሴ ነው (የግምገማ ተጠሪውን ሳይሆን የሪፍሬሽመንት ክፍሉን!)  
ከምሬ ነው--- ለምን አጭር የቡና ሰዓት አይኖርም? (“ኖሮ አያውቅም ወይም አልተለመደም” እንዳትሉኝ!) ለነገሩ ብትሉኝም አልቀበልም፡፡ ይኼውላችሁ---- ድሮ የሌሉ አሁን የተጀመሩ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ እናም ----- ድሮ የቡና ሰዓት የሌለው ምናልባት ዘመኑ ስለማይጫጫን ይሆናል፡፡ አሁን ግን ይጫጫናል እያልን ነው፤ስለዚህ መፍትሄ የግድ ነው፡፡ በእርግጥ መፍትሄው ትኩስ ቡና ብቻ ነው እያልኩ አይደለም፡፡ ትኩስ ቀልድ ሊሆንም ይችላል፤ ዋናው ነገር ከእንቅልፍና ከድብርት ስሜት ማነቃቃቱ ነው፡፡ ያለዚያ እኮ ጠ/ሚኒስትሩ ከስንት አንዴ ተገኝተው የሚያቀርቡት ሪፖርትና ማብራሪያ ከንቱ ሆነ ማለት ነው! (እንቅልፍ ወስዶት “ገና” እንዳመለጠው ትንሽ ልጅ!)  እናላችሁ --- አባላቱ ሁሉን ነገር በንቃት እንዲከታተሉ ከፈለግን coffee break ቢኖር አይከፋም፡፡ አሊያም ደግሞ አንድ ሁለት ሞቅ ያለ ሳቅ የሚያጭሩ ቀልዶች ያስፈልጋሉ - በየመሃሉ፡፡ (ፓርላማው ቀልድ ለምዷል እኮ!) የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር (ነፍሳቸውን ይማረውና) በቀልድና በተረብ እያዋዙ ነበር እንዲህ ያሉ የፓርላማ ጉባኤዎችን የሚመሩት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም የግድ ኩምክና ይጀምሩ እያልኩ አይደለም፡፡ ግን ደግሞ የተዋዛ “ስፒች” የሚፅፍላቸው----ከንግግራቸው ጋር የሚጣጣም ተረትና ምሳሌ የሚነግሯቸው ----- ሰሞነኛ ቀልዶችን የሚያሰሟቸው ቀልድና ጨዋታ አዋቂዎች አማካሪዎች ያስፈልጓቸዋል፡፡
   በዲሞክራሲ የበለፀጉ አገራት መሪዎችም እኮ እንኳንስ ቀልድ ንግግርም ተለማምደውና ሰልጥነው ነው የሚቀርቡት፡፡ (በጎውን መኮረጅ ክፋት የለውም ተብሎ የለ!) እኔ የምለው----የእንግሊዝ ፓርላማን የክርክር ሥርዓት አይታችሁልኛል? ቀውጢ እኮ ነው! (እንኳን ሊጫጫን የተኛንም ይቀሰቅሳል!) ይገርማችኋል----ወረቀት ይዞ የሚያወራ እንኳን አታዩም! ሁሉም በቃሉ ነው የሚያንበለብለው፡፡
በነገራችሁ ላይ ---- የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም እርጋታ ይማርከኛል፡፡ (መማረክ መብቴ ነው!)  የቱንም ያህል የሚያስቆጣ አስተያየት ቢሰነዘርም በቁጣ ማዕበል አይወሰዱም፡፡ ተገቢ የመሰላቸውን መልስ ተረጋግተው ይሰጣሉ እንጂ! ይሄ መቼም በልምምድ የሚመጣ አይመስለኝም - በተፈጥሮ እንጂ!! (በምንም ይምጣ ብቻ ተመችቶኛል!)
ወደ ዋናው ጉዳይ ስንመጣ፣ በፓርላማ ብቸኛው የተቃዋሚ ተወካይ የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ---ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ ተመርኩዘው በአሽሙር የተጠቀለለ አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡ “አሁንም የትራንስፎርሜሽንና እድገት እቅዱ በዋና ዋና መስኮች ይሳካሉ ብለው ያስባሉ ወይንስ ልምድ ተቀስሞበታል ብለን እንድንወስድ ነው የሚፈልጉት?” (ቃል በቃል ሳይሆን መንፈሱን ነው!) በዚህ አስተያየት ትንሽ ሳይከፉ አልቀሩም - ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡ (ተከፉ እንጂ ተቆጡ አልወጣኝም!)
ጠ/ሚኒስትሩ ከሰጧቸው መልሶች መካከል ይበልጥ ትኩረቴን ይበልጥ የሳበው--- “አንድ ተማሪ 10 ጥያቄዎች ቀርበውለት 8ቱን በትክክል መልሶ ሁለቱን ቢሳሳት እንዴት ሰነፍ ይባላል?” ሲሉ የጠየቁበት ነው፡፡ በእርግጥ ራሳቸው ናቸው የመለሱት፡፡ “ጎበዝ ተብሎ ይበረታታል እንጂ!” በማለት፡፡ (መንፈሱን እንጂ ቃል በቃል አይደለም!) እንግዲህ ተማሪው ኢህአዴግ ነው ወይም ኢህአዴግ መራሹ መንግስት፡፡ አስሮቹን ጥያቄዎች ያወጣውም ራሱ ኢህአዴግ ነው፡፡ ፈተናውን የተፈተነውም ኢህአዴግ ነው፡፡ ፈተናውን ያረመውም ራሱ ኢህአዴግ! እኔ የምለው--- ኢህአዴግ ራሱ ፈተና አውጥቶ፣ ራሱ ተፈትኖ፣ ራሱ አርሞ---- እንዴት ይችለዋል? (እርማቱ የምር ከሆነ ማለቴ ነው!)
ከዚያው ከፓርላማ ጉዳይ ሳንወጣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ መብራት ኃይል ኮርፖሬሽንን የገለፁበት መንገድ አንጀቴን እንዳራሰው ልገልፅ እወዳለሁ፡፡ (መብራት መጥፋቱ ስለማይቀር አንጀቴን ላርስ እንጂ!) “ደንበኞችን ማበሳጨት ዓላማው ያደረገው መብራት ኃይል!” ሲባል የሰማሁ ይመስለኛል፡፡ “ማበሳጨት” ግን አይገልፀውም “ማጨስ” የሚለው ይሻላል!! አንድ ጥያቄ አለኝ - ባለፈው አንድ ወር ለአፍታም ቤቱ ወይም ቢሮው መብራት ጠፍቶበት የማያውቅ ካለ ይሸለማል (ቤተመንግስትና የከፍተኛ ባለሥልጣናት መኖሪያ ቤቶችን አይመለከትም!)
በነገራችሁ ላይ ---- ሰሞኑን በኢቴቪ የሰማሁት አንድ ዜና እንዴት  በግርምት እንደሞላኝ አልነግራችሁም!  በኢትዮጵያ ውስጥ የግል ሚዲያውን የሚያሰራ በቂ ነፃነት መኖሩን የአፍሪካ ሚዲያ መሪዎች ድርጅት አረጋገጠ ይላል- ዜናው፡፡ ወደ ኋላ አስር አመት ግድም ተመልሼ አንድ ነገር ላስታውሳችሁ፡፡ ይሄም በ97 የምርጫ ቀውስ ማግስት በኢቲቪ የሰማሁት ዜና ነው፡፡ ትዝ ይላችሁ እንደሆነ ---- ለሁለት ይሁን ለሶስት ቀን ታክሲዎች አድማ መተው ነበር (ያኔ ማህበርና ታፔላ አልነበረማ!) ሲበቃቸው ወደ ሥራ ገቡ፡፡ አገልግሎት ሲሰጡም ዋሉ፡፡ ማታ ታዲያ ኢቴቪ ምን ብሎ ቢዘግብ ጥሩ ነው? “ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ ታክሲዎች አገልግሎት ሲሰጡ እንደዋሉ ሮይተርስ ዘገበ” አይገርማችሁም --ኢቴቪ በገዛ አገሩ የተከሰተውን ሁነት የመዘገብ ልበሙሉነት አጥቶ ሮይተርስን በእማኝነት አቀረበ፡፡ (በእርግጥ የተቃዋሚው ጎራ “ዓይንህን ላፈር” ብሎት ነበር!) የሰሞኑም ዜና ተመሳሳይ ነው፡፡ “አላልኳችሁም----የግል ሚዲያዎች ለመስራት የሚያስችል ነፃነት አላቸው---ይኸው የአፍሪካ ሚዲያ መሪዎች መሰከሩ” የሚል ዓይነት መንፈስ ያዘለ ነበር - የኢቴቪ ዜና፡፡ እኔ የምለው---- እኛ ባለቤቶቹ ብንጠየቅ አይሻልም ነበር፡፡
እውነቱን ልንገራችሁ አይደል----በፍርድ ቤት የተመሰከረብን ነው የመሰለኝ፡፡ ከስንት አገር አውሮፕላን ተሳፍሮ መጥቶ “ለመስራት የሚያስችል ነፃነት አላችሁ” ብሎን ሄደ (ሳንጠይቅ እኮ ነው!) ለነገሩ እኛ ባንጠይቅም የሚጠይቅ ይጠፋል ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ ራሳቸውን “የቀለም አብዮት ተከላካዮች” አድርገው የሚቆጥሩ አንዳንድ አገር በቀል ማህበራት ጠይቀው ሊሆን ይችላል፡፡ ለማንኛውም ግን የነፃነቱም ይሁን የአልቦ ነፃነቱ ባለቤቶች እኛ ነን፡፡ በተለይ መንግስትና ኢህአዴግ ስለኛ ነፃነት ከእኛው ቢሰሙ ነበር የሚሻላቸው፡፡ (እውነቷን ከፈለጉ ማለቴ ነው!) የሚገርመው ደግሞ ምን መሰላችሁ? ባለፈው ህዳር ወር ላይ የአፍሪካ ሚዲያ መሪዎች ጉባኤ በአፍሪካ ህብረት  ሲካሄድ፣ የራሳችንን ጉዳይ ራሳችን እንጂ ምዕራባውያን እንዲናገሩልን አንፈቅድም የሚል ሃሳብ ሲንፀባረቅ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ የግል ሚዲያ በነፃነት እየሰራ ይሁን አይሁን የሚያረጋግጡልን ግን እነሱ ሆነው አረፉት! (ያሳዝናልም ይገርማልም!)  

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
የበዓሉ ሰሞን እንዴት አደረጋችሁሳ!
ስሙኝማ…የክትፎ ‘ግርግር’ ተጀመረ አይደል! ኮሚክ እኮ ነው…‘የተመሳሰል’ ‘የተቀላቀል’ ዘመን፡፡ ለታመመች ሚስቱ አሞክሲሊን መግዣ መሥሪያ ቤት የብድር ጥያቄ አግብቶ ከቢሮ ቢሮ የሚመላላሰው ሰው የክትፎ ቤት ‘ግርግር’ ዋና ተዋናይ ሆኖ ስታዩት ግራ አይገባችሁም!
ስሙኝማ… ይሄ “ምርታችንን አስመስለው የሚሠሩ ስላሉ...” “ተመሳሳይ ምርቶች ገበያ ውስጥ መግባታቸውን ስለደረስንበት…” ምናምን የሚሉ ማስታወቂያዎች አልበዙባችሁም! አሁን፣ አሁንማ “ተመሳስሎ ያልተሠራው የትኛው ምርት ነው?” ልንል ምንም አልቀረን! ልክ ራሱን የቻለ ‘አስመስሎ የመሥራት ኢንዱስትሪ’ የተፈጠረ ነው የሚመስለው፡፡ እኔ የምለው…ይሄ ዕቃ አስመስሎ የሚያትመው ‘3ዲ’ ማተሚያ ገባ እንዴ!
እኔ የምለው… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የመመሳሰል ነገር ካነሳን አይቀር የባሰበት ደግሞ የሰዉ ‘ተመሳስሎ መሠራት!’ እናላችሁ… ‘ተመሳስለን የተሠራን’….በዝተናል!
ታዲያላችሁ….ዘንድሮ ተመሳስለው የተሠሩ ‘ቦተሊካ—ተኮሮች’ ብዛት ግርም የሚላችሁ ነው። ልክ ነዋ… ‘ቦተሊካ—ተኮር’ መሆን በተዘዋዋሪ “እዩኝ፣ ከእናንተው ጋር ነኝ…” አይነት ማመልከቻ ማስገባት ነዋ! ዘንድሮ የ‘ሥራ ችሎታ’ን ከማሳየት ይልቅ ‘ታማኝነትን ማሳየት’ አቋራጭ መንገድ እየሆነ ነው ስለሚባል ራሳችንን ‘አመሳስለን እየሠራን’ ያለን መአት ነን፡፡
እናላችሁ…የአለቆቻችንን ንግግሮች እንዳለ…አለ አይደል… ከእነማስነጠሱ ጨምረን የምንደግም ‘ተመሳስለን የተሠራን’ መአት ነን፡፡ ምክንያቱም ማስመሰል የታማኝነት ማሳያ ሆኗላ! “እየተከናወኑ ያሉ ሁለንተናዊ የዴሞክራሲ፣ የፍትህና መልካም አስተዳዳር እንቅስቃሴዎች አጠናከሮ ለማስቀጠል…” ምናምን አይነት በሚል በተመሳሳይ ማሸጊያዎች የተጠቀለልን ተመሳስለን የተሠራን ‘ቦተሊካ—ተኮሮች’ እየበዛን ነን፡፡
ስሙኝማ… በተለይ ይሄ ዘመን ያመጣው የፖለቲካ ‘ቋንቋ’ መጠቀም ተመሳስሎ የመሠራት ዋና መለያ ሆኗል፡፡ ገና ለገና የእሱ መሥሪያ ቤት ሁለት ተጨማሪ ኮምፒዩተሮች ስለገዛ “ታማኝ ነኝ” ለማለት “መንግሥታችን በሚያካሂደው ያልተቆጠበ የልማትና ዕድገት…” ምናምን የሚል ተመሳስሎ የተሠራ አትርሱኝ ባይ አለቃ ሞልቶላችኋል፡፡
ሠላሳ ተጨማሪ ሠራተኛ ለሚያስፈለገው መሥሪያ ቤት ሦስት የሥራ ማስታወቂያ ብቻ ስላወጣ… አለ አይደል… “መንግሥት ሀገሪቱን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ጋር ለማሰለፍ በሚያደርገው ያለሰለሰ ጥረት፣ የሥራ ሀይላችንን በማጠናከር ለልማቱ የበኩላችንን አስተዋጽኦ እያደረግን ነው…” ምናምን አይነት ተመሳስሎ መሠራት ሞልቶላችኋል፡፡
ደግሞላችሁ…ተመሳስለው የተሠሩ የስኑፒ ዶግ፣ ፊፍቲ ሴንት ምናምን ቀሺም ‘ፎቶ ኮፒዎች’ ግልባጮች አሉላችሁ፡፡ በአንቺ ሆዬ ቅኝት ቅልጥ ያለ የራፕ ምት በማስገባት ራስን ‘ከአማሪካን ዘፋኞች’ አመሳስሎ የመሠራት ነገር ሞልቶላችኋል፡፡ ስሙኝማ… በራፕ ስልት የሚያስገቧቸው እንግሊዘኛ ‘ግጥሞች’ የሚሉት ተሰምቷችሁ ያውቃል! የምር… እኔ እንግሊዝኛ ቋንቋን እንዲህ ‘ዋጥ ማድረግ’ የሚቻል አይመስለኝም ነበር! ቂ…ቂ…ቂ…
እናላችሁ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ተመሳስለን የተሠራን ‘አገር ወዳዶች’ ደግሞ ሞልተንላችኋል፡፡ አለ አይደል… የ‘አደባባይ’ አገር ወዳድነታችን የሚኖረው ጓዳችን እስከሞላ…ቦርሳችን እስከሞላ…ካዝናችን እስከሞላ ድረስ የሆንን ተመሳስለን የተሠራን ‘ፓትሪዮቶች’ አለንላችሁ፡፡ አገር መውደድ ማለት …‘እንደ ሰዉ’ የሀገር ልብስ መልበስ…‘እንደ ሰዉ’ አዳራሽ በባንዲራ ማድመቅ… በኳስ ስናሸነፍ መጨፈር፣ ስንሽንፍ ማኩረፍ …የሚመስለን የዘመኑ የ‘ተመሳሰል’ና ‘ተቀላቀል’ ጨዋታ ህጎች ‘የገቡን’ ሞልተናል፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… የአገር ወዳድነት ነገር ካነሳን አይቀር የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ። ያለፈው ቅዳሜ በወጣው የ‘ፋክት’ መጽሔት እትም ላይ ሌፍተናንት ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ ያሉት ደስ አይልም! ስለ አሸፋፈታቸው ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ… “ጥይቱን በራስዎ ገንዘብ ገዝተው ነው የሚዋጉት?” ብሎ ሲጠየቃቸው…“በራሴ ገንዘብ ነው እንጂ! ሀገር አይደለችም እንዴ ታማ የተኛችው! እናት አይደለችም ሀገር! እናትህ ታማ መድኃኒት ግዛላት ስትባል ገንዘብ ስጪኝ ትላታለህ?” ብለው ነው የመለሱለት፡፡
እናማ…እንዲህ አይነቱ ሀገር ወዳድነት ነው የናፈቀን! እንዲህ አይነቱ ሀገር ወዳድነት መዳከሙ ነው ሀገርን ታማ ከምታቃስትበት አልጋ ላይ ቀና የሚያደርጋት፡፡
እናማ…“ሀገር አይደለችም እንዴ ታማ የተኛችው?” ብሎ የሚቆጭ ትውልድ ያብዛልንማ!
ደግሞላችሁ…በ15 ዓመታቸው አርበኝነት የመግባታቸውን ምክንያት ሲጠየቁ ምን ቢሉ ጥሩ ነው…“አሀ! እኔ በቁሜ እያለሁ ጣሊያን ሀገሪቱን ቅኝ ሲያደርጋት ዝም ብዬ ማየት አለብኝ?” ነው ያሉት፡፡
አንድዬ እንዲህ አይነት የሀገር ጥቃት ማየት የማይፈልጉ ዜጎችን በብዙ እጥፍ ይፍጠርልንማ!
ስሙኝማ…ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…የጥንቷን ‘ጥልያን’ አይነት ሌላ ባላጋራ ቢመጣ…አለ አይደል…እንኳን ሁላችን ‘መጠቃቱ ሊያንገበግበን’ ቀርቶ…‘ዕንቁላል ለመሸጥ’ የሚደረገው ግፊያ በሪዮ ካርኒቫል የሚገኘውን ህዝብ በብዙ እጥፍ ብዛት የሚበልጥ ይመስለኛል፡፡ ዘንድሮም ቢሆን ዘዴው ይለዋወጥ እንጂ…‘ዕንቁላል እየተሸጠ’ እንደሆነ “ጠርጥር፣ ከገንፎ ውስጥ አለ ስንጥር…” አይነት ነገር የሚያስብሉ ነገሮች አሉላችሁ፡፡
እናላችሁ…ከተጨዋወትን አይቀር…
ለሰማው ዕፁብ ነው ላየውም ይደንቃል
እንዴት አንድ አገር ሰው በማበል ያልቃል
የምትል የጥንት ስንኝ አለች፡፡ ‘ተመሳስሎ መሠራት’…አለ አይደል…ማበልም ነው፣ ማዕበልም ነው፡፡ ‘አባዮች’ ሆነን በማዕበል ከመወሰድ ያትርፈንማ!
ደግሞላችሁ…ተመሳስለን የተሠራን…‘የፈረንጅ አፍ የሚቀናን’ አለንላችሁ— አለ አይደል…የቋንቋ ችሎታችን… ዝቅ ሲል ከ“ዋው!” ከፍ ሲል ከ“ኢንተረስቲንግ ነኝ” የማያልፍ፡፡ (ስሙኝማ…እግረ መንገዴን… ለፈረንጆቹ እንዲቀርብልን የምንፈልገው ሀሳብ አለን.. “ዋው!” የሚሏት ቃል የ‘ፈረንጅ አፍ’ ጆከር ትባልልንማ! ልክ ነዋ…“ዋው!” ያልገባችበት ነገር አለ እንዴ! “ዋው!” የማይል ቢኖር የቡቲክ አሻንጉሊቶች ብቻ ይመስሉኛል፡፡ እንደውም ቦሶቻችን “ዋው!” የምትለውን ቃለ መጠቀም ከጀመሩ፣ ምን አለፋችሁ፣ ወደ መካካለኛ ገቢ መጠጋታችንን ልንጠረጥር እንችላላን፡፡ ቂ..ቂ…ቂ…)
ታዲያላችሁ…ተመሳስለው የተሠሩ…በመሥሪያ ቤታቸው ፍቅር ብን ያሉ አሉላችሁ፡፡ ስብሰባ ላይ ዋና ‘ሀሳብ’ አቅራቢዎች (‘ሀሳባቸው’… “መንግሥት ዲሞክራሲ ስላጎናጸፈን ምስጋና ይግባውና… ምናምን ከማለት ባያልፍም) የሆነ ዝግጅት ሲኖር ዋና አፋሽ፣ አጎንባሽ የሚሆኑ…ከአእምሯቸው ይልቅ ጆሮዎቻቸው ሥራ የሚበዛባቸው…ተመሳስለው የተሠሩ ሞልተውላችኋል፡፡
እናማ…ተመሳስሎ የመሠራት ችግር በተለያዩ ምርቶች ላይ ብቻ ሳይሆን በእኛም ላይ ነው። እናማ…“በእኔ አምሳል ተመሳስለው የተሠሩ ሰዎች መኖራቸውን ስለደረስኩበት ወዳጆቼ እንዳትታለሉ…” ምናምን አይነት ማስታወቂያዎች የምንሰማበት ጊዜ አይመጣም አይባልም፡፡ ሀገሯ ‘ጦቢያችን’ ነቻ!
ስሙኝማ…ከፍ ብለን በጠቀስነው ቃለ መጠይቅ ላይ ሌፍተናት ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ ያሏት አንድ ግሩም ነገር አለች…“እንኳንም የሀገሬን ውለታ የበላሁ እኔ አልሆንኩ፣” ነው ያሉት፡፡ በዚህ ዘመን ስንቶቻችን ነን እንዲህ ማለት የምንችለው?
ሀገሬ ጥሪኝ፣ ሀገሬ ጥሪኝ
እመጣልሻለሁ መቼም በራሪ ነኝ፣
እመጣለሁና ቀኑ ቢሞላልኝ
ሀገሬን አደራ ሀገሬን አቆዩኝ፣
…………
ልቤን ሀሳብ ገብቶት፣ እየሰረሰረው
አትስጡብኝ አለ አገሬንም ለሰው፡፡
ተመሳስሎ በመሠራት ሳይሆን በእውነተኛ ንጹህ ስሜት እንዲህ አይነቶቹን ዜማዎች ደጋግመን የምናዜምበትን ጊዜ ያቅርብልንማ! የ‘ተመሳሰል፣’ ‘ተቀላቀል’… ዘመን ዕድሜ አይርዘምብንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Published in ባህል

           የአገራችን የመንግስት ቴሌቪዢንና ሬድዮ፣ ለበርካታ ሳምንታት በራሺያና በዩክሬን “ድራማ” ዙሪያ ያለማቋረጥ የሚያሰራጩት ነገር፣ ለአገራችን ምን አይነት መዘዝ እንደሚያስከትል የተገነዘቡት አይመስልም። “ድራማው”፣ የሚያሳዝንና የሚያሳስብ እንጂ፣ የሚያስቦርቅና የሚያስፈነድቅ ድራማ አይደለም። በጠበኛ እብሪት የተለከፈው የራሺያ መንግስት  ዋና አቀናባሪነትና ስፖንሰርነት በሚመራው በዚሁ ድራማ፤ ዩክሬን በጎሳና በሃይማኖት ስትሰነጣጠቅ እየታየ ነው። እና፣ ይሄን እያዩ በደስታ ጮቤ መርገጥ ተገቢ ነው?
የውጭ ጠበኞች የሚያሴሩባትና የውስጥ ጣጣዎች የሚያስቸግሯት አገርኮ ዩክሬን ብቻ አይደለችም። ኢትዮጵያም፣ ከሩቅና ከቅርብ፣ በጎሳም ሆነ በሃይማኖት ሰበብ “እንበጥብጣት” የሚሉ (የራሺያ አይነት)የውጭ አገር ጠበኞች አሉባት። አንዳንድ የግብፅ ባለስልጣናት ኢትዮጵያን ለመበጥበጥ ሲዝቱ ሰምተናልኮ። ለብጥብጥ የሚሆን ሰበብ ደግሞ ሞልቷል። አገራችን፣ከጎሳና ከሃይማኖት ጋር የተቆራኙ ነባርና ኋላቀር የውስጥ ጣጣዎች የሉባትም እንዴ? እንደ ዩክሬን ለአደጋ የሚያጋልጡ የአገራችን ጣጣዎች ጥቂት አይደሉም። የራሺያ መንግስትና የኬጂቢ ኮለኔል የነበሩት ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ በዩክሬን ላይ የሚያካሂዱት ዘመቻ ድብቅ ሚስጥር አይደለም። የግብፅ መንግስት፣ የሶማሌ ክልል ተወላጆች እንዲገነጠሉ በማሴር፣ “የራሳቸውን እድል በራሳቸው ይወስኑ” እያለ ዘመቻ ቢያካሂድ እንደማለት ነው። ከኢትዮጵያ ጎን የሚሰለፍ አለኝታ ይኖራል? ምናልባት፣ ዩክሬንንም ከጥቃት የሚያድን አለኝታ መንግስት አይኖር ይሆናል። ግን፣ አነሰም በዛ ከጎንሽ ነን ብለው የሚከራከሩላት የአሜሪካና የአውሮፓ ወዳጅ መንግስታትን አላጣችም። ኢቴቪ ይህንንም ሲያወግዝ ነው የምንሰማው። በራሺያ ሴራ ዩክሬን ስትሰነጣጠቅ እያየን ብንቦርቅ፣ በራሳችን ላይ መዘዝ መጋበዝ እንደሆነ እነኢቴቪ እንዴት አልተረዱትም?
በእርግጥ የራሺያና የዩክሬን ጉዳይ፣ እዚሁ ለአገራችን የራሱ አንደምታና ትርጉም እንደሚኖረው እነ ኢቴቪ አያውቁም ማለቴ አይደለም። ትርጉም እንዳለው ስለሚያምኑማ ነው፤ ነገሩን እንደራሳቸው ጉዳይ የእለት ተእለት ዘመቻ ያደረጉት። በእርግጥ፣ “ዜና ወይም ዘገባ አሰራጨን እንጂ ዘመቻ አላካሄድንም” ሊሉ ይችላሉ። ግን፤ዜና ወይም ዘገባ ማሰራጨት ሌላ! በራሺያ ፍቅር የታወረ እስኪመስል ድረስ፤ በዩክሬንና በምዕራብ አገራት ላይ ጭፍን የጥላቻ ዘመቻ ማራገብ ደግሞ ሌላ! የኢቴቪ ዜናዎችና ዘገባዎች፣ በስሜት የጦዘ “ቲፎዞ” ከሚሰነዘረው ጭፍን አስተያየት አይለዩም። ጭፍን አስተያየት፣ በዜና ወይም በዘገባ ስም ሲቀርብ ምን ይባላል? “ፕሮፓጋንዳ” ይባላል። ሌላ መጠሪያ ስም የለውም። ለዚያውም ማንንም የማይጠቅምና ሁሉንም የሚጎዳ ቀሽም ፕሮፓጋንዳ!
ፕሮፓጋንዳ በተፈጥሮው፣ እውነተኛ መረጃዎችን በማጥፋትና በማግለል፣ በማጣመምና በማድበስበስ ትክክለኛ ግንዛቤ እንዳይፈጠር ስለሚያግድ ጎጂ ነው። ከረዥም ጊዜ አንፃርም፣ የእውነትን ክብር በመሸርሸር፣ በሁሉም ተቀናቃኝ ቡድኖች ዘንድ ጭፍንነት እየተስፋፋና ስር እየሰደደ እንዲሄድ ያደርጋል። የኢቴቪ ፕሮፓጋንዳ ቀሽምነት ግን፣ ከዚህም ይብሳል። ብዙ ሰዎች ወደ ፕሮፓጋንዳ የሚሮጡት፣ ውሎ አድሮ እንደሚጎዳ ስለማያውቁ፤ ወይም ደግሞ ጎጂነቱ ባይጠፋቸውም ለማያዛልቅ የአጭር ጊዜ ጥቅም እጅ ስለሚሰጡ ነው። የኢቲቪ ፕሮፓጋንዳ ግን፤ቅንጣት ታህል የአጭር ጊዜ ጥቅም የለውም። ከንቱ ድካም ነው። “ከንቱ ድካም” ሲባል ግን፤ እርባና ቢስነቱን ለመግለፅ ያህል እንጂ፤ “ምንም ውጤት አያመጣም” ለማለት አይደለም። መጥፎ ውጤት ያስከትላላ - አገሪቱንና ነዋሪዎቿን ለአደጋ በሚያጋልጥ የተሳሳተ አስተሳሰብ የተቃኘ ፕሮፓጋንዳ ነዋ። “እርባና ቢስ ነው” የምለውም፤ ኢቴቪ ወደ ፕሮፓጋንዳ እንዲገባ የሚገፋፋ መነሻ ሰበብ የለም ማለቴ አይደለም።
ለግንዛቤ የሚያስቸግር ውስብስብ ጉዳይ አይደለም። በጭላንጭልም ቢሆን አይኑን በመክፈት ለአንድ አፍታ ከጭፍንነት ለመራቅ ፈቃደኛ የሆነ ሰው፣ በቀላሉ ሊገነዘበው ይችላል። የራሺያ መንግስት በዩክሬንና በሌሎች ጎረቤት አገራት ላይ የሚሸርበው ሴራና የሚያካሂደው ዘመቻ፤ የኤርትራ መንግስት በጎረቤቶቹ ላይ ከሚፈፅማቸው ጠበኛ ድርጊቶች ብዙም አይለይም። ይሄ አጥፊ ተመሳሳይነት ለኢቴቪ የማይታየው ለምን ይሆን? የፕሮፓጋንዳው መነሻ ሰበብስ ምንድነው? የሁለቱም ጥያቄዎች መልስ አንድ ነው -“የቀለም አብዮት”!
መንግስት፣ ኢህአዴግ ወይም የመንግስት ሚዲያ፣ ለበርካታ አመታት በ“ቀለም አብዮት” ላይ ብቻ ክፉኛ ስላፈጠጡ፤ ዛሬ ዛሬ ሁሉም ነገር “የቀለም አብዮት” እየሆነ ይታያቸዋል። ሊያሳስባቸው አይገባም ማለቴ አይደለም። የስልጣን ጉዳይ ነውና ቢያሳስባቸው አይገርምም። እንዲያውም፤ እነሱን ብቻ ሳይሆን፤ ማንንም ሰው ሊያሳስበው ይገባል። “የመጣው ይምጣ” ወደሚል ተስፋ ቢስነት ለዘቀጠ ሰው ወይም “ሳይደፈርስ አይጠራም” ከሚል አላዋቂነት ላልተላቀቀ ሰው ካልሆነ በቀር፤  ነባሩን አስተዳደር የሚያናጋ እንቅስቃሴ ሲፈጠር ማንኛውም ጤናማ ሰው በጥሞና ማሰብ ማሰላሰል ይኖርበታል። “ለውጥ” በቁንፅል ለጤናማ ሰው በቂ አይደለም። የተሻለ ነገር ለማምጣት የሚያስችል መሆን አለበት - “ለውጥ”። “የመጣው ይምጣ” ብሎ በጭፍን መደናበር ግን ጤንነት አይደለም። “የባሰ ቢመጣስ?” የሚል ጥያቄ አለና ነው። ጤናማና ብልህ ሰው፤ ነገሮች ጥርት ብለው እንዲወጡ ለማድረግ ከመነሻው አስበው፣ መላ አበጅተውና መድረሻቸውን አቅደው ይጣጣራሉ እንጂ፤ “መጀመሪያ ይደፍርስ፤ ያኔ የደፈረሰውን ለማጥራት እናስብበታለን” ብለው በጭፍን አይገቡበትም። “ከደፈረሰ በኋላ ባይጠራስ?” የሚል ጥያቄ አለና ነው።
በተጨባጭ ያለውን እውነታ ከመነሻው በአግባቡ መገንዘብ፤ ወደፊት የሚመኙትን የተሻለ ሕይወት በቅጡ ለይቶ መድረሻውን ማወቅ፤  ከመነሻ ወደ መድረሻ የሚጓዙበት ትክክለኛውን መንገድ መምረጥ ያስፈልጋል። ተጨባጩን እውነት፣ የለውጡን መንገድ እና የታለመውን ሕይወት፣ ... ሦስቱንም አስተሳስሮ ማሰብ እንደሚያስፈልግ ከተገነዘብን፤በዘመናችን “የቀለም አብዮቶች” ተብለው የሚጠሩ “የለውጥ እንቅስቃሴዎችን” ሁሉ በጅምላ እየፈረጁ በደፈናው መደገፍም ሆነ መቃወም፤ ከአላዋቂነት ወይም ከጭፍንነት የዘለለ ትርጉም እንደማይኖረው ይገባናል። ለምን? “የቀለም አብዮቶች” ሁሉ እኩል አይደሉም። የብዙ ሰዎችን (የሕዝብን) ትኩረት በመማረክ የሚጀመሩ የለውጥ እንቅስቃሴ ከመሆናቸው በስተቀር፤ ብዙም ተመሳሳይነት የላቸውም። በተነሱበት እውነት፣ በመረጡት መንገድና ባለሙት የሕይወት ግብ ይለያያሉ።
ለምሳሌ የመጀመሪያው የቀለም አብዮት ነው ተብሎ በኢህአዴግ መፅሔት የተጠቀሰው፤ “velvet revolution”ን ተመልከቱ። በ1982 ዓ.ም ቼኮዝላቫኪያ ተብላ ትጠራ በነበረችው አገር የተካሄደ የለውጥ እንቅስቃሴ ነው። ያኔ የነበረው እውነታ ምን ነበር? አፈና በሰፈነበት የኮሙኒስት ስርዓት ውስጥ፤ በነፃነት ማሰብና ሃሳብን መግለፅ፣ ማንበብና ሃሳቦችን መቀበል ወንጀል ነበር። የሰዎች ስራ፣ ምርት፣ ንብረትና ኑሮ በሙሉ በመንግስት ቁጥጥር ስር ነው። ከኮሙኒስት ፓርቲው ውጭ ሌላ አማራጭ የፖለቲካ ሃሳብ መሰንዘርም ሆነ ፓርቲ ማቋቋም ወንጀል ነው። የመምረጥም ሆነ የመመረጥ መብት የለም። በአጠቃላይ፤ በስለላ የታመቀ፣ በአፈና የደነዘዘ፤ በመንግስት ቁጥጥር የተራቆተና የደኸየ ኢኮኖሚ፤ በራሽን የታጠረና መላወሻ ያጣ ኑሮ፤ ... በአጠቃላይ እያንዳንዱ ሰው ፓርቲንና መንግስትን በባርነት የሚያገለግል አቅም አልባ፣ ምስኪንና ክብረቢስ ፍጥረት ተደርጎ የሚቆጠርበት የውርደት ሕይወት ነበር። በአጭሩ በደርግ ዘመን በኢትዮጵያ ውስጥ ከነበረው ሕይወት ብዙም አይለይም። የነፃነትን ጭላንጭ የሚዘጋ፣ የብልፅግናን እድል የሚሰብር፣ የእኔነትን ክብር የሚያኮላሽ የኮሙኒዝም ስርዓት።
ደግነቱ፤ ሰው ብርቱ ነው። ከፍርሃትና ከአፈና የመላቀቅና የነፃነትን አየር የመተንፈስ ሰውኛ ፍላጎት ጠፍቶ አይጠፋም። መላወሻ ከሌለው የመንግስት ጭሰኝነትና ከንብረት አልባነት ተገላግሎ ንብረት የማፍራትና ብልፅግናን የመቋደስ ምኞት ተዳፍኖ አይቀርም። የካድሬና የቀበሌ ሊቀመንበር ሎሌ፤ የሚሊሻና የታጣቂ መጫወቻ ከመሆን ተገላግሎ፣ አንገትን ቀና አድርጎ ሕይወትንና ሰላምን የማጣጣም ህልም ብን ብሎ አይሰወርም።
በኮሙኒስት ስርዓት ውስጥ የነበረው እውነታ፤ በአፈናና በፍርሃት፣ በዝርፊያና በድህነት፣ በሸክምና በውርደት የተሞላ ኑሮ ነው። ወደፊት የተመኙት ሕይወትና ያለሙት መድረሻስ ምን ነበር? የነፃነት አየርን መተንፈስ፣ የብልፅግና እድልን መቋደስና የሕይወትን ጣዕም ማጣጣም ነው። በእርግጥም፤ ከአብዮቱ በኋላ፤ የግል ሚዲያና የፖለቲካ ምርጫ ተጀመረ። የግል ንብረትና የቢዝነስ ስራ ተፈቀደ። አንገትን ቀና አድርጎ የመራመድ የእፎይታና የሰላም መንፈስም ተገኘ። በእርግጥ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ነፃነት እንዲሁም ሰው የመሆን ክብር በተሟላ ሁኔታ ሰፍኗል ማለት አይደለም። ግን ከድሮው በእጅጉ በእጅጉ ይሻላል። በከፊልም ቢሆን፤ ወዳለሙትና ወደተመኙት መድረሻ የሚያሸጋግር መልካም ለውጥ እውን ሆነ ማለት ነው። እንዴት?  በምን አይነት የለውጥ እንቅስቃሴ? አደባባዮችንና ጎዳናዎችን በሚያጥለቀልቁ የተቃውሞ ሰልፎች ነው፣ የቀድሞው አምባገነን የኮሙኒስት ስርዓት ፈርሶ ለውጥ የመጣው።
እንግዲህ፤ የአገሬው ሰዎች ምን አይነት ሁኔታ ውስጥ እንደነበሩ ቃኝተናል - መነሻቸውን። የመጣውን ለውጥ ተመልክተናል - መድረሻቸውን። የተጓዙበትን አቅጣጫ አይተናል- መንገዳቸውን። ከዚህ ውስጥ ምን የሚያስወቅስ እንከን አገኛችሁበት? በተቃውሞ ሰልፍ ከአምባገነንነት መላቀቃቸውና ለውጥ ማምጣታቸው ያስወቅሳቸዋል? ደም ሳይፈስ በተቃውሞ ሰልፍ ብቻ መልካም ለውጥ መገኘቱ መታደል ነው። የሚያስሞግስ እንጂ የሚያስወቅስ አይደለም። ሌላው ቀርቶ፤ የመቶ ሺዎችን ህይወት የቀጠፈና የሚሊዮኖችን ኑሮ ያናጋ ጦርነት ተካሂዶ በኢትዮጵያ ለውጥ መምጣቱስ ያስወቅሳል እንዴ? ነውጠኛና አመፀኛ ብለን ኢህአዴግን ማውገዝ ተገቢ ነው? በጭራሽ። በእርግጥ፣ በጠባቡም ቢሆን ሃሳብን የመግለፅና በምርጫ የመሳተፍ እድል ባለበት አገር፤ “ለውጥ አመጣለሁ” ብሎ ወደ ጦርነት መግባት ተገቢ አይደለም። ሃሳብን የመግለፅና ምርጫ የማካሄድ እድል እየተዘጋ ካልሄደ በቀር፣ እንኳን በጦርነት ይቅርና በጎዳና ሰልፎች መንግስትን ለመለወጥ መነሳትም፤ ተገቢ የማይሆንበት ጊዜ አለ። በተለይ ደግሞ፣ ከነባሩ ስርዓት በእጅጉ የተሻለ መልካም ለውጥ እንደሚመጣ በእርግጠኝነት የማናውቅ ከሆነ፤ ነገር ማደፍረስ ጥቅም የለውም። በስሜት ደረጃ ጥሩ ጥሩ ነገሮችን ከመመኘት ባሻገር፤ የምንመኛቸውን ነገሮች እውን ለማድረግ ምን አይነት ስርዓት እንደሚያስፈልግ በትክክል ካላወቅንና መድረሻችንን በቅጡ መለየት ካቃተን፤ “የለውጥ እንቅስቃሴ” ሁሉ ከንቱ ይሆናል። የእነ ግብፅ እና የእነ ሊቢያ አብዮቶች፤ እንዲሁም በጆርጂያና በዩክሬን የተካሄዱ ፀረ ራሺያ አብዮቶች በዚህ ጎራ የሚመደቡ ናቸው። በነባር ችግሮች እየተማረሩ የተሻለ ነገር ከመመኘት በስተቀር፤ መድረሻቸውን በግልፅ ለይተው ባለማወቃቸው፤ብዙም ሳይራመዱ ለቀውስ ተዳርገዋል።
ግን ከእነዚህም የባሰ ሞልቷል። የተሻለ ነገር በመመኘት ሳይሆን ወደ ባሰ ክፉ ስርዓት ለመጓዝ የሚካሄዱ የለውጥ እንቅስቃሴዎች አሉ። የሶሪያ እና የሴንትራል አፍሪካ ቀውሶችን መጥቀስ ይቻላል። በራሺያ አቀናባሪነት ዩክሬን ውስጥ እየተካሄደ ያለው ፀረ ምዕራብ አገራት እንቅስቃሴም፣ ከዚሁ የጥፋት ጎራ የሚመደብ ነው።
ፀረ ራሺያ አቋም የያዙ ዩክሬናዊያን አደባባዮች ማጥለቅለቅ “ለውጥ” ለማምጣት ተቃውሞ ሰልፍ ሲያካሂዱ፤ መንግስት በወሰደው እርምጃ ከመቶ በላይ ሰዎች ተገድለዋል። ከዚህ በኋላ ነው፤ ፕሬዚዳንቱ ከስልጣን ተባርረው መንግስት የተለወጠው። ኢቴቪ ይህንን ምን ይለዋል? መፈንቅለ መንግስት ብሎ ይጠራዋል። በምርጫ ስልጣን የያዘ መንግስት የፈረሰው፣ “የቀለም አብዮተኞች” ባካሄዱት መፈንቅለ መንግስት ነው በማለት ኢቴቪ በየእለቱ ሳያወግዝ አያልፍም። በመንግስት ስለተገደሉት ሰዎች አንዳችም የትችት አስተያየት አይሰነዝርም።
በራሺያ የሚደገፉ ዩክሬናዊያን፣ በክሬሚያ እና በሌሎች ምስራቃዊ ክልሎች ምን አይነት “የለውጥ እንቅስቃሴ” እንደሚያካሂዱ ተመልከቱ። በተቃውሞ ሰልፍ አልያም በታጣቂ ቡድኖች አማካኝነት፣ አደባባዮችን ብቻ ሳይሆን የመንግስት መስሪያ ቤቶችን በሃይል ይቆጣጠራሉ። መንግስት መስሪያ ቤቶቹን ለማስለቀቅ ሲሞክር አምስት ሰዎች ተገድለዋል። ኢቴቪ ስለተገደሉት ሰዎች ሲናገር፤ 5 የነፃነት ታጋዮች ተገድለዋል በማለት ነው የገለፀው። ለማንኛውም “የነፃነት ታጋዮቹ” በሃይል የተቆጣጠሯቸው የመንግስት መስሪያ ቤቶች አልተለቀቁም። እናም በራሺያ የሚደገፉት “የቀለም አብዮተኞች” ፤ በምርጫ ስልጣን የያዙ የክልልና የከተማ አስተዳደሮችን ለማፍረስ ችለዋል። በእርግጥ ኢቴቪ እነዚህን፣ የቀለም አብዮተኞች አይላቸውም። የራስን እድል በራስ የመወሰን መብታቸውን ለማስከበር የሚጠይቁ የነፃነት ታጋዮች እያለ ነው የሚጠራቸው።
ክሬሚያ የተሰኘው የዩክሬን ክልል እንዲገነጠልና ወደ ራሺያ እንዲጠቃለል የተደረገውም፤ እነዚሁ በራሺያ የሚደገፉ “የቀለም አብዮተኞች” (በኢቴቪ አጠራር “የነፃነት ታጋዮች”) ባካሄዱት የተቃውሞ ዘመቻ አማካኝነት ነው - በምርጫ ስልጣን የያዘውን አስተዳደር በሃይል በመቆጣጠርና በማፍረስ።
በአንድ በኩል፤በምርጫ ስልጣን የያዙ ፕሬዚዳንት በተቃውሞ አመፅ ከስልጣን ሲባረሩ፤ “በቀለም አብዮተኞች የተፈፀመ ትልቅ ወንጀል ነው” ተባለ። እሺ። በሌላ በኩል፤ በምርጫ ስልጣን የያዙ የክልል ፕሬዚዳንቶችና የከተማ አስተዳዳሪዎች፤ በተቃውሞ አመፅ ሲባረሩስ? “በነፃነት ታጋዮች የተገኘ ትልቅ ድል ነው” ተባለ። ታዲያ እንዲህ አይነቱ ፕሮፓጋንዳ እዚያው እርስ በርሱ የሚጣፋ ከንቱ ድካም አይደለምን? ለአጭር ጊዜ የሚያገለግል ጥቅም እንኳ የለውም። ይልቅ ለረዥም ጊዜ የሚዘልቅ ጉዳት አለው። እንዴት በሉ። በራሺያ አቀናባሪነትና ድጋፍ፣ የክሬሚያ ክልል ከዩክሬን ተገንጥሎ ወደ ራሺያ መጠቃለሉ፤ በኢቴቪ ቤት “የነፃነት ትግል” ነው። ይህንን ሁኔታ ወደ አገራችን አምጥተን እንየው።  ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ “በቀለም አብዮት” መንግስት ተለወጠ እንበል። ከዚያስ? ከዚያማ ልክ የራሺያ መንግስት እንዳደረገው፤ የሶማሊያ መንግስትም የኢትዮጵያ አካል የሆነው የሶማሌ ክልል እንዲገነጠል ድጋፍ ይሰጣል። የክልሉ መስተዳድር ስልጣን የያዘው በምርጫ ቢሆንም፤ በሶማሊያ መንግስት ስፖንሰር አድራጊነትና በተቃውሞ ሰልፈኞች አማካኝነት እንዲፈርስ ይደረጋል እንበል። ከዚያም በሶማሊያ መንግስት ወታደራዊ አለኝታነት ተማምነው፤ የኢትዮጵያን ህገመንግስት በሚጥስ መንገድ የሶማሌ ክልል እንዲገነጠል በምርጫ አስወስነናል ይላሉ፤ ወደ ሶማሊያ እንዲጠቃለልም ያደርጋሉ። ምናባዊ ታሪክ ነው። ነገር ግን ከእውነተኛው ታሪክ ጋር ያን ያህል አይራራቅም። እስከዛሬ አልተሳካም እንጂ፤በርካታ የሶማሊያ ፖለቲከኞች ለረዥም አመታት ያቀነቀኑትን አቋም እንዲሁም በተደጋጋሚ ያካሂዱትን ወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ ሙከራ ስንመለከት፤ ምናባዊው ታሪክና እውነተኛው ታሪክ ተቀራራቢ መሆናቸውን ለመገንዘብ አይከብድም።
ለነገሩ ከላይ እንደጠቆምኩት፤ የኤርትራ መንግስት ጠበኛ ባሕሪዎችንም መመልከት ይቻላል። ለወጉ ያህል እንኳ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲንቀሳቀሱ የማይፈቅድ፣ ሌላው ቢቀር ለወጉ ያህል እንኳ ዜጎች በምርጫ እንዲሳተፉና ሶስት አራት ነፃ ጋዜጦች እንዲታተሙ እድል የማይሰጥ፣ ከጎረቤቶቹ ሁሉ የባሰ የለየለት አምባገነን መንግስት ነው። ነገር ግን፤ የተለያዩ ክልሎችን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል የሚፈልጉ ቡድኖችን እያሰባሰበ ይደግፋል፤ እያስታጠቀ ያሰማራል - የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት በሚል መፈክር እያሳበበ። እንዲህ አይነቱ ዘመቻ እንዴት እንደ ነፃነት ትግል ይቆጠራል?       
 አንድ የጥንት አባባል አለ - “ምን ያለበት ምን አያወራም” የሚል አይነት። አባባሉን ከዘመናዊ አኗኗር ጋር እንዲጣጣም ከፈለግን፤ “መስተዋት ውስጥ የተቀመጠ፣ ስለ ድንጋይ ውርወራ አያወራም” ልንለው እንችላለን። በመላው ዓለም ብዥታና ግርግር በበዛበት ዘመን ነው የምንኖረው። ከኋላቀርነትና ከግጭት ያልተላቀቀ አህጉር ውስጥ ነው ያለነው - ለዚያውም ለበርካታ አስርት አመታት ባልረገበ ጥላቻና ባልተቋረጠ ግጭት የሚታመሰው የአፍሪካ ቀንድ!  በዚያ ላይ፤ ከኋላቀር የጎሳና የሃይማኖት ጣጣዎች ጋር ስትዳክር ዘመናትን ያስቆጠረች ናት - አገራችን። እዚህ ውስጥ ሆነን፤ የድንጋይ ውርወራን እያዳነቅን ባናወራ ያሻላል።

      ባለፉት ጥቂት ዓመታት እንጀራ ፍለጋ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተዘዋውሬአለሁ፡፡ ከዋናው መንገድ ወደ ውስጥ እስከ መቶ ኪ.ሜ እና ከዚያም በላይ የመግባት ዕድሉ ነበረኝ፡፡ ከማሕበራዊ፣ ባሕላዊም ሆነ ፖለቲካዊ ትዝብቶች ይልቅ አትኩሮቴ የሚሳበው በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ነው፡፡ ከሥራዬ ጋር ተያያዥነት ያለው እሱ ነው፡፡ ይሄም አጭር መጣጥፍ በየቦታው ያየሁትን የሕዝቡን አኗኗር በጨረፍታ  የሚያሳይ ነው፡፡
በመጀመሪያም ከአዲስ አበባ በሁሉም አቅጣጫ ስወጣ፣ ትላልቅ ከሚባሉት ከተሞቻችን ውጪ ብዙዎቹ ከተሞች አስፋልት ወለድ እንደሆኑ አየሁኝ፡፡ ሰንጥቋቸው የሚያልፈውን ዋና መንገድ ዳር እና ዳር ተከትለው፤ እንደ ልብስ ስፌት በሰንሰለታማነት የተቀመጡ አሮጌ የአፈር ቤቶች ቅጥልጥል ተመለከትሁ፡፡ የሚገርመው ነገር የብዙዎቹ ከተሞች መመሳሰል ነው፡፡ በእያንዳንዷ ከተማ የምታየው ነገር አሁን ያለፍካትን ከተማ ደግመህ እያቋረጥክ እንዲመስልህ ሊያደርግ ሁሉ ይችላል፡፡ በሁሉም ቦታ የማታጣቸው ትዕይንቶች አሉ … ጸጉራቸውን እየጠቀለሉና ብጉራቸውን እያፈረጡ ሥራ ፈትተው የተቀመጡ አንድ አምስት ወጣቶች (ከእንግሊዝ ክለቦች ማልያ አንዱን የለበሰ ቢያንስ አንድ አይታጣም)፤ የጀበና ቡና አቦል አቦሉን እየጠጡ ጫት የሚያኝኩ ጎልማሶች፤ የጨርቅ ኳስ (አንዳንዴም ባዶ የፕላስቲክ ጠርሙስ እንደ ኳስ እየተጠቀሙ) የሚጫወቱ ሕፃናት (ከመካከላቸው ቢያንስ አንዱ የዋልያዎቹን ማልያ ይለብሳል)፤ ሦስት አራት ባለ ሁለትና ሦስት ፎቅ ጅምር ሕንጻዎች፤ ብዙ አሮጌ የአፈር ቤቶች ቅጥልጥል፤ እናም ደግሞ አጠገባቸው ዝነኛዋ ሾፌሮች ምግብ ቤት/ሆቴል!
በመላ አገሪቱ በእኩል መጠን የተከፋፈለ ነገር ቢኖር ያፈጠጠና ያገጠጠ ድህነት እንደሆነ አይቻለሁ፡፡ ከአፈርና አየሩ፤ ከባሕሉም፣ ከማሕበራዊ ሕይወቱም ሆነ ከፖለቲካው በላይ ያስተሳሰረን ተመሳሳይ ኢኮኖሚያዊ ደረጃችን ይመስለኛል፡፡ “አንድነታችን በድህነታችን” ያለው “የአክሱም ጫፍ አቁማዳ” ገጣሚም ልክ ሳይሆን አይቀርም …
“… እኔ ወንድሞቼ ሁላችን … ሁላችን
ከባዶ አቁማዳ ነው የሚዛቅ ፍቅራችን
ይህ ነው አንድነታችን
ይህ ነው ባህላችን
ዘመን ማዛጋቱ በያንደበታችን …”
(ደበበ ሰይፉ፣ ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ)
ገጠር ሲባል የተንጣለለ ለምለም መስክ፤ የጎመራ አዝመራ፤ አረንጓዴ ተራሮች፤ የማይነጥፉ ጅረቶች፤ በጥጋብ የሚቦርቁ ጥጆች፤ ከሁሉም በላይ ደግ ሕዝብ እና ይሄን የመሳሰለው ነገር በአዕምሮዬ ይመላለሳል፡፡ በእርግጥ በእውንም ቢሆን ከዚህ የሚቀራረቡ ቦታዎችን አይቻለሁ፡፡
በየደረስኩበት ገጠር መንደር ፎቶግራፍ የማንሳት ልማድም አለኝ፡፡ በተለይ የሕጻናቱን፡፡ ታዲያ በጉዞዬ መጨረሻ ወደ አዲስ አበባ ተመልሼ ፎቶዎቹን ለወዳጆቼ ሳሳያቸው፣ የትኛው የየት አካባቢ ልጅ መሆኑን መለየት እንኳ አይችሉም፡፡ በአብዛኛው የተቀዳደደ ልብስ፣ ባዶ እግር፣ አመድ የመሰለ ፊት---- ከሰሜን ደቡብ ተመሳሳይ ሕጻናት! ይባስ ብሎ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚገኙ ሕጻናት ደግሞ በጠጠር መንገዱ ላይ አቧራ እያስነሳ ከሚከንፈው መኪናህ መሳ ለመሳ፣ ድክ ድክ እያሉ እጃቸውን ለልመና ይዘረጉልሃል፡፡ በእርግጥ ሳንቲም አይደለም የሚጠይቁህ፤ እሱን የሚጠይቁማ ሀብታም ለማኞች ናቸው፡፡ ከገንዘብም ያነሰ  ነገር ይለምኑሃል… “ሃይላንድ! ሃይላንድ! ሃይላንድ!” አንድ ሰሞን በሥራ ባልደረባዬ መካሪነት ለመስክ ሥራ በወጣሁ ቁጥር የተወሰነ እስክርቢቶ ይዤ መሄድ ጀመርኩ፡፡ በመጀመሪያው ቀን አንድ አምስት ለሚሆኑ ሕጻናት አደልኩ፡፡ ሆኖም ባዶ የፕላስቲክ ጠርሙስ፤ “ሃይላንድ”፤ ስሰጣቸው ውጤት አገኘሁ፡፡ አብዛኛው የገጠር ሕጻን፣ ብዕርና ባዶ ኮዳ ብታቀርብለት ሁለተኛውን ይመርጣል፡፡ ምን ያድርግ፤ “ሃይላንዱን” የሠሩት በመጀመሪያ ብዕሩን የመረጡ ሰዎች መሆናቸውን ማን ገልፆለት!
ሴቶቹ በጀርባቸው ሸቀጥ ብጤ ያዘሉ፤ እርቃን እግራቸውን የሆኑ፡፡ አንተ መኪና ውስጥ ሆነህ እንኳ ከበርካታ ደቂቃዎች በኋላ የምትደርስበት የገበያ ቦታ በጊዜ ለመድረስ ያዘግማሉ፡፡ (አንዳንዶቹ ቆም ብለው “ሊፍት” እንድትሰጣቸው እየጠየቁህ፣ መኪናህ ውስጥ ቦታ ቢኖርም አይተህ እንዳላየ ሆነህ ታልፋቸዋለህ)፡፡
አርሶ አደሩ ጎተራው እንደሞላ፤ ቃል እንደተገባለትም በቀን ሦስቴ በልቶ ማደር እንደጀመረ የመንግሥት ሚዲያዎች ይነግሩሃል፡፡ እርግጥ ነው በርካቶች ሚሊየነር ሆነዋል፡፡ በተቃራኒው ያሉትን ድሆች አርሶ አደሮችን ለጊዜው እንተዋቸውና (ማንስ ስለእነኚህ ያወራል!?) የብዙዎችን የሀብታም አርሶ አደሮችን በራፍ አንኳኩቻለሁ፡፡ ገጠር ሲባል በአዕምሮዬ ውስጥ የሚመላለሰው ሰዉ ደግነት እንዳለ ነው! የሰው ደግነት ብቻ ሳይሆን አኗኗሩም እንዳለ ነው! የሚመገቡት ምግብ ማሻሻያ እንዳልተደረገበት በግልፅ ይታያል፡፡ ቤታቸውን አይተህ ሚሊየነሩ አርሶ-በሌ ሁሉ፣ በቂ ሀብት እያለው እንኳ ሣይሞት አፈር የገባ መሆኑን ትረዳለህ፡፡ የገንዘብ እንጂ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ አልተሰራም፡፡ የሀሳብ ድህነት ደግሞ በሳንቲም መቅጨልጨል የምታስደነብረው አውሬ ነገር አይደለም፡፡
መደረግ ያለበት- የገጠሩ ሰው ጥሪት ከመቋጠር በዘለለም ሊቀስማቸው የሚገቡ የኑሮ ክህሎቶች እንዳሉ ማሳየት ነው፡፡ በቀላሉ ራሳቸው በሚያድሩበትና በከብቶቻቸው ጋጣ መካከል ልዩነት እንዲፈጥሩ፤ ተሸላሚ አርሶ አደር ተብለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፊት ሲቀርቡ ብቻ ሳይሆን ሁሌም ንጹህ እንዲለብሱ፤ ነገ አድገው አገር የሚረከቡ ልጆቻቸውን እንዲንከባከቡ፤ የተመጣጠነ ምግብ እንዲመገቡ (ሦስት ጊዜ መመገብ ብቻ ሳይሆን ቢያንስ ሶስት ዓይነት ምግብን እንዲመገቡ) የሚያስችሏቸው ስልጠናዎች እንዲያገኙ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ተገንዝቤአለሁ፡፡

Page 3 of 13