ስስት፣ ቅንዓትና ምቀኝነት በየትኛውም የዓለም ክፍል የተጠላና የሚያስጸይፍ ተግባር ነው። ሆዳምነትም እንደዚሁ የስስት ታላቅ ወንድም በመሆኑ የትም ቢሆን ተቀባይነት የለውም። ከዚህም የተነሣ አባቶቻችን (እናቶቻችን) ተረት ሲተርቱ “አልጠግብይ ሲተፋ ያድራል”፣ “ከስስታም አንድ ያንቀው አንድ ይወድቀው”፣ “ሆዳም ከአልሞተ አያርፍም”፣ “ሆዳም ሰው ፍቅር አያውቅም”፣ “ሆድ አምላኩ”፣ “ለሆዳም በሬ ጭድ ያዝዝለታል”። “አህያ ሆድ”፣ “ዘተር ሆድ”፣ “ቅርጫት ሆድ” … እያሉ በመተረት ስስታምነትን ይኮንናሉ፡፡ ብዙ ሰው በተለይ ምግብ ተዘጋጅቶ በቀረበ ጊዜ የዓይን ስስት አለበት፡፡ እጠግብ ስለማይመስለው ሁሉ ነገር ለእርሱ እንዲሆን ይመኛል፡፡ ሌላ ተጋሪ ሰው ሲመጣበት ዓይኑ ደም ይለብሳል፡፡ በተጻራሪው ደግሞ አንዳንድ ሰው፤ ሰው በልቶ የሚጠግብ ስለማይመስለው ያለውን ሁሉ ያለ ስስት ያቀርባል። ብቻውን የሚበላ ሰው በማኅበረሰባችን በእጅጉ የተጠላ በመሆኑ “ብቻውን የበላ ብቻውን ይሞታል።” ተብሎ ይተረትበታል፡፡
በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አብዛኛውን ጊዜ ስስትና ሆዳምነት ጎልቶ የሚታየው በቤተክርስቲያን አካባቢ ነው፡፡ አንዳንድ ካህናት፣ ዲያቆናትና መነኮሳት በስስት ልጓም የታሠሩ ስለሆኑ በዕለት መክፈልት፣ መሀራና ተዝካር ጭምር ሲጣሉና ሲደባደቡ ይውላሉ፡፡
መሪ ጌታ ዋለና መሪጌታ ተገኘ የተባሉ ሁለት መሪጌቶች በአንድ ቤተክርስቲያን ውስጥ ይኖሩ ነበር፡፡ ነገር ግን ሁለቱም እርስበርሳቸው ስለሚናናቁ ሁልጊዜ በነገር ይጎሻሸማሉ፡፡ አንድ ቀን ከሰዓት በኋላ ቅዳሴ ተቀድሶ ከደጀሰላም ውስጥ መሀራ ሲበሉ መሪጌታ ተገኘ ሆዳም ኖሮ እየጠቀለለ ቶሎ ቶሎ እንጀራውን ሲጎርስ መሪጌታ ዋለ ይመለከታል፤ ዋለም ተገኘን አይቶ ለመወዳደር ቶሎ ቶሎ ይጎርሳል።
በዚህ ጊዜ መሪጌታ ተገኘ የመሶቡን እንጀራ ሲያገባድደው ተመልክቶ “ብሉ ወንድሞቼ መብል እንደተገኘ ነው” ይላል፡፡ መሪጌታ ተገኘም “አዎ ያውም በዋለ ሆድ” ብሎ የመልስ አጠፌታ ሰጠ፡፡”
የለጋስነት፣ የቁጥብነትና የርኅራኄ መንፈስ ያላቸው ሌሎች ካህናትና ዲያቆናትም የስስታሞችን ድርጊት በምክርና በተግሳጽ ጭምር ለማርገብ ከሚያደርጉት ጥረት ባሻገር፣ ቅኔ ጭምር በመቀኘት ስስትንና ሆዳምነትን ይታገላሉ፡፡
በአንድ ወቅት አንድ የቅኔ መምህር፣ ላሊበላን ሊሳለም ወደሮሃ ይሄዳል፡፡ በላሊበላ አካባቢ ደግሞ ሐዋ ሚካኤልና ድቡኮ ማርያም የተባሉ ቦታዎች አሉ። እንግዳው የቅኔ መምህር በእነዚህ ቦታዎች በሚገኙ ቤተክርስቲያኖች በየጊዜው አገልግሎት ቢሰጥም መሀራ (ድግስ) ቤተክርስቲያን ውስጥ በቀረበ ጊዜ ካህናቱ ደጀ ሰላሙን እየዘጉ ይበላሉ። ከሌላ ቦታ የመጣን ካህን በምንም መንገድ ስለማይጋብዙ፣ እንግዳው የቅኔ መምህር ሙሉ ቤት መወድስ ተቀኝቶባቸው ወደ ሀገሩ ተመልሷል፡፡
ከቅኔው ውስጥ የማስታውሰው ዋዌውን (ከግማሽ በኋላ ያለውን) ነውና እነሆ፡-
“ስስትኒ ዘወልደ ነዌ ዘሐዋ ሚካኤል አስመኮ፡፡
ተወልደ ላሊበላ ወልኀቀ በድቡኮ፡፡”
ትርጉሙ በሐዋ ሚካኤል የተንሰራፋው የነዌ ልጅ ስስት የተወለደው ላሊበላ፣ ያደገው በድብኮ ነው ማለት ነው፡፡  
እንደዚሁም በምዕራብ ጎጃም ውስጥ በምትገኘው በደብረ መድኃኒት ጨጎዴ ሐና፣ አንድ ስስታም ቄስና አንድ ሆዳም ዲያቆን በአንድ ቀን ይሞታሉ። ሊቀ ሊቃውንት ያሬድ ሺፈራውም ከዚሁ ሁኔታ በመነሣት የሚከተለውን መወድስ ቅኔ ዘርፈዋል፡፡
አንተ ቄስ የመክፈልቱ አለቃ፣
ወ አንተ ዴማስ የቤተልሔም ጎናዴ፡፡
እርሻችሁ ቀፈት ታርሶ የደቀቀው ለስንዴ፡፡
በብዛት ከናንተ ተነሥቶ ተሰጠ ለዳንዴ፡፡
ተጠንቀቅሂ አያ ተማሪ እንዳታሳስትህ በዘዴ
ብዙዎችን ቄሶች አስታለችና መክፈልት ወረገዴ።
ዝኒ ስስት የመጋዣዎች ነጋዴ፤
አጋሰስ አጋሰሱን አነሣው በጨጎዴ፡፡
ወረገዴ አግብታ የፈታች ጋለሞታ ስትሆን አጋሰስ ለጭነት ፈረስ የሚሰጥ ስያሜ ነው፡፡ ብዙ የሚበላና የሚያጋፍር ሰውም አጋሰስ ተብሎ ይሰደባል፡፡
በአንዳንድ ስስታም ቄሶችና ሆዳም ዲያቆናት ተርታ፣ ሆዳም መነኩሴዎችንም በየደብሩ ማግኘት አይገድም፡፡ መሪጌታ ልሣነ ወርቅ የተባሉ ሊቅ የአንዲት ሆዳም መበለት ድርጊት አስገርሟቸው የሚከተለውን ዋዜማ ተቀኝተውባታል፡፡
(ቅኔና ቅኔያዊ ጨዋታ ለትዝታ 1997 ገጽ 20)
ሖረት እሙሐይ
ለዘዚአሃ ኅብስት ወለዘዚአሃ እንጎቻ፡፡
እሙሐይ ከርሠ እንቲአሃ አኮኑ ስልቻ፡፡
ወአዕጋሪሃ ኀነብር በላዕለ ሠለስቱ ጉልቻ፡፡
ወለመደት ካዕበ ብቻ ለብቻ፡፡
እስመ ዛቲ የሰይጣን ኮርቻ፡፡
በእርግጥም ሊቁ እንዳሉት፣ ሆዳምና ስስታም ሰው የሰይጣን መፈናጠጫና መቀመጫ (ኮርቻ) ነው፤ ለማለት ይቻላል፡፡ በሊቁ በልሳነወርቅ ትዝብት መሠረት መነኩሴይቱ ጾም፣ ጸሎት፣ ስግደት አታውቅም፡፡ በመሸ በነጋ እግሮቿን በሦስት ጉልቻዎች ላይ አነባብራ ማስቀመጥ፣ በየዕለቱ እንጎቻና ቂጣ እየጋገረች ለብቻዋ ስለምትበላ ሆድዋ እንደ ስልቻ የተቆዘረ፣ ዐመለ ቢስ ጠባየ ልክስክስ፣ የሰይጣን ፈረስ እንደሆነች እንረዳለን፡፡
በከተሞች አካባቢ ብዙ ጊዜ የተለመደው የብፌ ግብዣ ነው፡፡ ታዲያ አንዳንድ ስስታም ሰው የማይበላውን ሁሉ ቆልሎና የራስ ዳሽን ተራራን አስመስሎ ከወሰደ በኋላ አንገዋልሎና ነካክቶ ይተወዋል፡፡ የሰውን ድግስም ያበላሻል፡፡ አንድ ወቅት ከፍተኛ የሆነ የመንግሥት ስብሰባ ከተደረገ በኋላ፣ በቤተ መንግሥት የራት ግብዣ ተደርጎ እንደነበር አንድ ጓደኛዬ አጫውቶኛል፡፡ በግብዣው ላይም ጋዜጠኞች ተጋብዘው ነበርና በወቅቱ የብፌው ድግስ ሁሉ አይቅረኝ የሚል ጋዜጠኛ፤ በሚያስፈራ ሁኔታ ምግብ በሳህኑ ላይ ቆልሎ ወደ መቀመጫው ሲራመድ ሰው ሁሉ እንደ ጉድ ይመለከተዋል፡፡ ከመኻል አንድ የኤሌክትሪክ ገመድ በድንት ሲጠልፈው የያዘው ምግብ በአማረው የቤተ መንግሥት ሥጋጃ ላይ ይበታተናል፡፡ እርሱም ለመውደቅ ይፍገመገማል፡፡ ወዲያው ሁኔታውን ሲከታተልና ሲታዘበው የነበረ አንድ ሰው “የት አባክ! ይበልህ! አንተም አብዝተኸው ነበር” ብሎ ገላመጠው አሉ፡፡
አድማሱ ጀንበሬ (1991 ገጽ 179) በአሳተሙት መጽሐፈ ቅኔ ዝክረ ሊቃውንት መጽሐፋቸው ላይ እንደጠቀሱት፣ አንድ ባለቅኔ “ሰዴ በተሰኘ ቦታ የሚኖሩ ካህናት በስስት ተጠምደው ተማሪን ቁራሽ እንጀራ ሲነፍጉት ተመልክቶ፣ እንዲህ ብሎ ፍርንዱስ መወድስ ተቀኝቶባቸዋል፡፡
“ዕሩቃነ መስጠት ልብስ ካህናተ ሰዴ፣
ወበምድረ ሰዴ ባቢሎን ሀገረ መከራ ክፋት፡፡
አልቦ ዘይዜከሮ፣
ለኤርምያስ ተሜ ዘአልቦ እራት፡፡
እስመ ይብሉ በአንድነት፡፡
ነፍስነ ትፃእ ምስለ ኢሎፍሊ መክፈልት፡፡
እጽሕፍሂ ዜና ግብሮሙ በብርዐ ልሳን ፅርፈት፡፡
እንዘ እብል እምኔሆሙ ይኄይሱ ከለባት፡፡
ካነሱብኝ ዘንድ ከፊቴ ግማሽ እንጀራ ካህናት፡፡
አምጣነ ከለባት ያተርፉ ሥጋ መዋቲ ለአራዊት”
ይህ ቅኔ ስለሰዴ ካህናት ስስት ያስረዳናል። ካህናቱ መስጠት የማያውቁ፣ በስስት ሸማ ተሸፋፍነው የሚኖሩ፣ ሀገራቸው የመከራና የክፋት እንደሆነ፣ ተማሪን የማያስታውሱና ለተማሪም የማይዘከሩ፣ ለአንዲት ቁራሽ መክፈልት ነፍሳቸው የምትወጣ እንደሆነች ያስገነዝበናል፡፡ ከእነዚያ ካህናትም ውሾት የተሻሉ እንደሆኑ፣ እንዲያውም ውሾች ለአራዊት ከሚበሉት ሥጋ እንደሚያተርፉ ትዝብቱን መነሻ አድርጎ ተቀኝቶባቸዋል፡፡
ካህናት ቀድዶ ማልበስ፣ ቆርሶ ማጉረስ ጥሩ እንደሆነ ቢሰብኩም ራሳቸው ግን አያደርጉትም። አንድ ካህን ዐውደ ምሕረት ላይ ቆመው ስብከታቸውን ሲዘሩ “ሁለት ልብስ ያለው አንዱን ይለብሰው ላጣ ይስጥ፣ አንድ እንጀራ ያለው ግማሹን ይጎርሰው ለተሳነው ያካፍለው” ሲሉ ያረፍዳሉ፡፡ ባለቤታቸው ለካ ስብከታቸውን ሲሰሙ ቆይተው ወደ ቤት እንደተመለሱ የባለቤታቸውን (የቄሱን ልብስ ከሁለቱ አንዱን) ለእኔ ቢጤ ይሰጣሉ፡፡ ሰባኪው ቄስ ድግሳቸውን ሲኮመኩሙ አረፋፍደው ወደ ቤት ሲመለሱ “አንቱየ ጧት በተስኪያን በተናገሩት መሠረት,ኧ ከእርስዎ ሁለት ልብስ አንዱን ለእኔ ቢጤ ሰጠሁት ቢሏቸው “በስመአብ ወወልድ መንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ! እኔ የሌሎችን አልኩ እንጂ የእኔንማ ለምን” ብለው ባለቤታቸውን ተቆጡ፡፡ ባለቤታቸውም በዚህ ተናድደው “ያንቱን ያንቱን ይተረጉሙ፣ የሌላውን ይደረግሙ” ብለው አሳፈሩዋቸው፡፡
ስስትና ሆዳምነት፣ እንደማይጠቅም ዓለምም ከንቱ መሆንዋን መሪጌታ አስካል (አድማሱ 1991 ገጽ 142) እንደዚህ በማለት በመወድስ ቅኔያቸው ይመክሩናል
ወዴት ያድር ይሆን ልብየ ያለም መንገደኛ፣
እደርሳለሁ ብሎ ተቤት መንገድ ሲጀምር በማታ፡፡
ይሆነው ይመስል ጥቅሞ የእነዓለሚቱ ጨዋታ፡፡
ጊዜው መሽቶበታልና ሳይሰፍር ከቦታ፡፡
ምንም ባትሰድ ሰው አሰናብታ፡፡
ጨዋታ ወዳድ ዓለም እያጫወተች ሁሉን በተርታ፡፡
እኛንም ሲያታልለን የዓለሚቱ ልጅ ደስታ፡፡
ገነት እናታችን ትቆየናለች ደጃፍዋን ዘግታ፡፡
ወይም አልያዝነ ጥቂት ከወንጌሉ ቃል ሸመታ፡፡
አዳም ያቆየው ተከራክሮ ገበያ ንስሐ ሳይፈታ፡፡
ይህንኑ የካህናትን ስስታምነትና ይሉኝታቢስነት የሚያመለክት ሌላ መወድስ ልጨምር፡፡
ቅኔው ፍርንዱስ (ግእዝና አማርኛ ነው፡፡ (አድማሱ 1991 ገጽ 36)
በአልባሰ አይሁድ ቅንዐት ወምቀኝነት፣
ዑፅፍታ ታንሶሱ ወታስተርኢ ኁብርታ፡፡
ልበ ካህናት ወለት እንተ ይእቲ አውታታ፡፡
ወሞተ በቅንዐት፣
ቀኛዝማች አማኑ አማኑኤል ምታ፡፡
ልበ ካህናት ጋለሞታ፣
እስመ ታቀንዖ ፈድፋደ ግራዝማች ደብዮን አግብታ፡፡  
ሞተሂ ያለ ጊዜው በጸሊዐ ቢጽ በሽታ፡፡
መርዓዊ ሀብተ ክህነት ዘተፍኀረ ለደስታ፡፡
ወእምላ ኩሉ ነገር ታሳዝነኛለች ይሉኝታ፡፡
አምጠነ ካህናት ቀተልዋ ወተቀብረት ሳትፈታ፡፡
ካህናት የአይሁድ ልብሳቸው በሆነው በቅንዐትና በምቀኝነት እንደተሸፈኑ፣ ልባቸው ይህንኑ የክፋት መጎናጸፊያ ተከናንባ እንደምትኖር ቀኛዝማች አማኑ የተባለው የምቀኝነትና የቅንዐት ባልዋም ከዚሁ ድርጊቱ የተነሣ እንደሞተ ቅኔው ይነግረናል፡፡
የካህናትን ልብም ሁሉን ከምታሰስት ጋለሞታ ጋር ያመሳስላታል፡፡ ግራዝማች ዳብዩ የዚህች የምታስቀናው የጋለሞታዋ ቅንዓት ባል እንደሆነ፤ ለደስታ የታጨው ሙሽራው የክህነት ሀብትም ጓደኛን በመጥላት በሽታ ተይዞ ያለጊዜው ሞተ ይለናል ባለቅኔው፡፡
ከሁሉም ይልቅ ይሉኝታ ታሳዝነኛለች፣ ምክንያቱም ካህናት ገድለዋት፣ ሳትፈታም ተቀብራለችና ይሉናል ሊቁ፡፡ ካህን እግዚአብሔርን ያገለገለ እየመሰለ፣ በሌላ ልቡ ገንዘብ ስለሚማርከው ይህንኑ አስመልክቶ አንድ ባለቅኔ እንዲህ ይለናል:-
ሥላሴ
ኢትክሉ ተቀንዮተ
ለእግዚአብሔር ወለንዋይ
ለዘይብል አምላክ ሰማዒ መቅድመ ኩሉ ታፍቅሮ፡፡
ለገብርከ አፍቅሮ ነዋይ ይእዜ ሠዓሮ፡፡
እመሰ ለወርቅ አፍቀርከ ወአስተባዛኅከ ክብሮ፡፡
እንዘ በጥንቁቅ ታነብሮ፡፡
አእምር አእምር አእምሮ፡፡
እመ ኮንከ ለንዋይ ገብሮ፡፡
ትርጉም (ካህናት ሆይ) ለእግዚአብሔር እና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም፡፡ ያለህን አምላክ ሰሚ ከሁሉ በፊት ታፈቅረው ዘንድ አገልጋይህ ገንዘብ መውደድን ዛሬ አሰናብተው፡፡ ወርቅን ብትወድ ክብሩንም ብታበዛ በጥንቃቄ እያኖርኸው የገንዘብ አገልጋይ እንደሆንህ ማወቅን እወቅ፡፡ “አንድ አገልጋይ ለሁለት ጌቶች መገዛት አይቻለውም፡፡` እንደተባለ እግዚአብሔርን እወድዳለሁ አከብራለሁ የሚል ሰው ገንዘብን በጣም የሚያፈቅር ከሆነ የእግዚአብሔር ወዳጅ ሊሆን አይችልም፡፡ በማለት ለገንዘቡ ሲንሰፈሰፍ የፈጣሪውን ትእዛዝ መፈጸም የሚያዳግተው መሆኑን ባለቅኔው ያስገነዝባሉ፡፡
በስስታም ካህናት ላይ በርካታ ቅኔዎች ተዘርፈዋል፡ ታላቁ ሊቅ ክፍለ ዮሐንስ በበኩሉ “እምከዊነ ካህን ይኄይስ ከዊነ ኖላዊ” የሚል መወድስ ሲቀኝ፣ አንድ ሌላ ባለቅኔ ደግሞ “ካህነ ቀላዋጭ ኢትናቅ ምድጥ ዋዕ ነጋዴ” ብሎ ተቀኝቷል። ክፍለ ዮሐንስ ካህን ከመሆን የከብት እረኛ መሆን እንደሚሻል ሲገልጥ ሌላው “ቀላዋጩ ስስታሙ ካህን የምጥዋን ነጋዴና አራሽ ገበሬን አትናቅ ያለእነርሱ መኖር አትችልምና” ብሎ በካህናት ላይ መወድስ ተቀኝቷል፡፡ እስቲ የክፍለ ዮሐንስን ቅኔ እንመልከት:-
እምከዊነ ካህን ይኄይስ ከዊነ ኖላዊ፣
ወጎለ እንስሳ ትትበደር እምቤተ መቅደስ ዐባይ፡፡
እስመ ቤተ መቅደስ ኮነት ቤተ ፊያታይ፡፡  
ወበላዕለ ኖሎት ኢሀለወ፣
በላዕለ ካህናት ዘሀሎ ዕከይ፡፡
ትእምርተዝኒ ከመንርአይ፡፡
በጎለ እንስሳ ሠረቀ ዘኢየዐርብ ፀሐይ፡፡
ወኖሎት ተዛውዑ ምስለ ሐራ ልዑል ሰማይ፡፡
ዓዲ እምቅድመዝንቱ እምከዊነ ኖሎት ወመራዕይ
ከመ ተጻውዑ ደምፀ እግረ ቃለ ዜና ሠናይ፡፡
ወልደ አንበረም ለምስፍና ወለቅብዐ መንግሥት ወልደ ዕሤይ፡፡
ከላይ የቀረበው ቅኔ ወደ አማርኛ ሲመለስ የሚከተለውን ይመስላል፡፡ ካህን ከመሆን እረኛ መሆን ይሻላል፡፡ የእንስሶች በረትም ከታላቅ ቤተመቅደስ ትመረጣለች፡፡ ቤተመቅደስ የሽፍታ ቤት ሆናለችና፡፡ የዚህንም ምልክት እናይ ዘንድ የማይጠልቅና የማይጨልም/ፀሐይ በእንስሳት በረት ወጣ፡፡  እረኞችም ከመላእክት ጋር አብረው ተጫወቱ። ዳግመኛም ከዚህ በፊት ከእረኞችና ከመንጐች ቦታ የአንበረም ልጅ (ሙሴ) ለመስፍንነት=@ የዕሴይም ልጅ (ዳዊት) ለመንግሥት ቅብዓት እንደተጠሩ የመልካም ወሬ ኮቴ ተሰማ፡፡
እረኞች ከብቶቻቸውን አሠማርተው እርስበርስ ከመጨዋወት በቀር ሌላ ተንኮል አያስቡም፡፡ ለጊዜው በጨዋታም ቢጣሉ ወዲያውኑ ይስማማሉ። መስማማታቸው ከቅንነት የተነሣ ሲሆን ክርስቶስ በእንስሳት በረት ሲወለድ እነርሱ (እረኞች) ከመላእክት ጋር አመስግነውታል፡፡
ከዚህም የተነሣ ባለቅኔው ከካህንነት እረኝነት፣ ከቤተመቅደስ በረት ይሻላል ይላሉ፡፡ ደግሞም ክርስቶስ ስለቤተመቅደስ ሲናገር፤ ቤቴ የጸሎት ቤት ነበር፤ እናንተ ግን የቀማኞችና የሌቦች ዋሻ አደረጋችሁት” ብሎዋል፡፡
ይህም እውነት ሊነገርባትና ሊሠራባት የተመሠረተችው ቤተመቅደስ፣ ማታለያና መሸቀጫ ስትሆን የከብቶች በረት ግን የክርስቶስ መወለጃና የመላእክት ማመስገኛ መሆኗን ባለቅኔው ገልጠዋል። (ካህሣይ ገ/እግዚአብሔር ብፁዓን እነማናቸው፡፡ 2004 ገጽ 53)  

Published in ጥበብ

የእነ ብ/ጄኔራል ጥላሁን ክፍሌ ታሪክ አሁንም ተድበስብሷል

“የቀድሞው ጦር” ማለት የምድር ጦር ማለት ነው? በሚል ርዕስ በገስጥ ተጫኔ በተጻፈው የሠራዊት ታሪክ ላይ ባለፈው ሳምንት አንድ ጽሑፍ ማስነበቤ ይታወሳል፤ ሆኖም የመጽሐፉ መጠን ዳጐስ ያለ በመሆኑና በተለይም እስካሁን ዕልባት ያልተገኘለት የእነ ብ/ጄኔራል ጥላሁን ክፍሌ የምጽዋ ውጊያ ታሪክ በደንብ ባለመታወቁ፣ እውነተኛውን እንድናውቅ፤ ብንችል ፍርጥ፣ ግልጥ አርገን በጉዳዩ ላይ እንድንወያይበት ሲባል የተለያዩ ማስረጃዎችን በማገናዘብ ተጨማሪ ጽሑፍ ማዘጋጀት አስፈልጓል።
ከጥር 30 ቀን 1982 እስከ የካቲት 9 ቀን 1982 ዓ.ም ምጽዋን ለመያዝ በሻቢያ በተካሄደው ዘግናኝ የማጥቃት ውጊያና ታሪካዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ሌት ከቀን ተዋግቶ ታሪክ የማይረሳው መሥዋዕትነት በከፈለው ሁለተኛው አብዮታዊ ሠራዊት ግዳጅ ውስጥ ምንጊዜም ቢሆን የማይረሱ ጥቂት ሰዎች አሉ፤ የተወሰኑት “በወገናቸው ላይ ክህደት ፈጽመው ለሻዕቢያ ያደሩና የሠራዊቱን የውጊያ ዕቅድና አሰላለፍ ምሥጢር ያጋለጡ” ተብለው በወቅቱ መንግሥት የተኮነኑ ሲሆን፣ ሌሎቹ ደግሞ “ለጠላት እጄን ከምሰጥ ሞቴ ይሻለኛል” ብለው ራሳቸውን በራሳቸው የሰዉ “ዳግማዊ ቴዎድሮሶች” ተብለው የተሞካሹት ናቸው፡፡
በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት የካቲት 9 ቀን 1982 ዓ.ም ምጽዋ በሻዕቢያ ሲያዝ ለ30 ዐመታት የተካሄደው ረጅምና መራራ “የእገነጠላለሁ፤ አላስገነጥልም” ጦርነት ማብቃቱ ገሃድ ነበር፡፡ በተገኘው የሻዕቢያ ድል በመንግሥት መከላከያ ሠራዊት ላይ ከባድ የአካልና የህይወት ዋጋ የመከፈሉን ያህል፣ የአዛዦችንና የመላ አገሪቱን ህዝብ ስሜት በእጅጉ የጐዳ ክስተት ነበር፡፡
ድል ሲገኝ “የታሪኩ ቀዳሚ ተዋናይ እኔ ነኝ” ብሎ መፎከር የተለመደውን ያህል እንዲህ አይነት ውድቀት ሲያጋጥም ደግሞ ዕርስ በርስ መነታረኩና እንደ ቆሰለ ጅብ መበላላቱ የተለመደ ነው፡፡ ለዚህም ነው በምጽዋ ግንባር የነበረው “መክት ዕዝ” ወይም 606ኛ ኮር ዋና አዛዥ በነበሩት ብ/ጄኔራል ጥላሁን ክፍሌ ላይ የዕርግማን ዶፍ ሲዘንብ የነበረው፡፡
ብ/ጄኔራል ጥላሁን ክፍሌ “የተማረክሁት ከአቅም በላይ የሆነ የጠላት ኃይል ገጥሞኝ እንጂ ወድጄና ፈቅጄ ለሻዕቢያ እጄን አልሰጠሁም” በማለት ቢያስተባብሉም በቀድሞ ጓደኞቻቸውና በአለቆቻቸው በኩል የተሰጣቸው ሥም ግን እጅግ የተለየ ነው፡፡ የሁለተኛው አብዮታዊ ሠራዊት ዋና አዛዥ የነበሩት ሜ/ጄኔራል ውብሸት ደሴ በቁጥር አሠ 2.1/ነ 142/102/82 የካቲት 11 ቀን1982 ዓ.ም ለጦር ኃይሎች ጠ/ኢታማዦር ሹም ለሌ/ጄኔራል አዲስ ተድላ በጻፉት ረጅም ደብዳቤ ውስጥ ስለተማረኩት ጄኔራሎች እንዲህ የሚል ሪፖርት አቅርበዋል፡-
“…በጠላት ከሚናፈሰው የሬዲዮ ወሬ ሰሞኑን እንደተከታተልነው ከሆነ፣ በኢትዮጵያ ሠራዊት ታሪክ አሳፋሪና ከፍተኛ የታሪክ ተወቃሽነት ክስተት ተከስቶአል፡፡ ይኸውም መንግሥትና ፓርቲያችን ከፍተኛ እምነትና ኃላፊነት ጥሎባቸው ለጄኔራል መኮንንነት ያበቃቸው ብ/ጄኔራል ጥላሁን ክፍሌና ብ/ጄኔራል ዓሊ ሐጂ አብዱላህ ከጠላት ወገን ሆነው ለጀግናው አብዮታዊ ሠራዊታችን የእጅ ስጥ ትዕዛዝ መልእክት እያስተላለፉ ይገኛሉ፡፡
“እነዚህ ሁለት ጄኔራል መኮንኖች ከቀይ ባሕር አውራጃ ውጊያ ቀደም ብለው ከጠላት ጋር የቅርብ ግንኙነት ሳያደርጉ እንዳልቀረና ጥላሁን ክፍሌ ቀይ ባሕር የሰፈረውን የወገን ጦር የሰው ኃይልና የጦር መሳሪያ አቀማመጥ ለጠላት ሳይሰጥ አልቀረም፤ እንዲሁም የ3ኛ ሜካናይዝድ ክ/ጦር አዛዥ የነበረው ከሃዲው ብ/ጄኔራል ዓሊ ሐጂ የክፍለ ጦሩን ጠቅላላ ምስጢር ለጠላት አሰልፎ ሳይሰጥ አልቀረም የሚል ከፍተኛ ጥርጣሬ አሳድሮብኛል፡፡
“የ6ኛ ነበልባል ክ/ጦር አዛዥ ብ/ጄኔራል ተሾመ ተሰማ እስከ የካቲት 9/1982 ዓ.ም 0800 ሰዓት ድረስ ከእኔ ጋር የሬዲዮ ግንኙነት እንደነበረውና ባስተላለፈልኝ መልእክት ጠላት አይሎ የምፅዋ ከተማን መቆጣጠሩንና ሁሉም ነገር ከአቅም በላይ እንደሆነባቸው ነግረውኛል፡፡ እርሳቸውም ቢሆኑ በአሁኑ ሰዓት ግንኙነት ስለተቋረጠ ይሙቱ ይኑሩ የታወቀ ነገር የለም…” የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ሜ/ጄኔራል ውብሸት ደሴ ምፅዋ በተያዘች በ3ኛው ቀን እንዲህ አይነት ደብዳቤ ይጻፉ እንጂ ለ10 ተከታታይ ቀንና ሌሊት የተካሄደው ውጊያ አሳሳቢ እንደሆነ፤ ተጨማሪ ጦር ካልተላከ የምፅዋ ጉዳይ ያለቀለት መሆኑ ሁሉ ሪፖርት ተደርጐላቸው ተግባራዊ አላደረጉም፡፡ በወቅቱ ደግሞ በኤርትራ ክ/ሀገር ውስጥ ከ300 ሺህ ያላነሰ ሠራዊት እንደነበር ይነገራል፡፡ ታዲያ እሳቸውስ ከታሪክ ተወቃሽነት ይድናሉ ማለት ነው? ጄኔራል ጥላሁን ክፍሌንና ብ/ጄኔራል ዓሊ ሐጂ አብዱላህን አስመልክተው የጻፉት ደብዳቤስ ምን ያህል እውነት ነው?
“በምፅዋ ጦርነት ከመጀመሪያ እስከመጨረሻ ተሳትፌ ተማርኬያለሁ” የሚለው ፶ አለቃ ታደሰ ቴሌ ሳልቫኖ፤ “አይ ምፅዋ” (1997) በሚል ርዕስ ባሳተመው መጽሐፉ እንደገለጠው፣ ብ/ጄኔራል ጥላሁን ከብ/ጄኔራል ተሾመ ተሰማ ጋር “አደረጉት” ያለውን የሬዲዮ ምልልስ እንዲህ ዘግቦታል፡-
“ስብሰባው እንደተበተነ የሬዲዮ ሠራተኛው ወደ ጄኔራል ተሾመ ተጠጋና ጄኔራል ጥላሁን እንደሚፈልጓቸው ገለጠላቸው፡፡ ሃንድሴቱን ሰጣቸውና መነጋገር ጀመሩ “ተሾመ ደህና ነህ?”  በማለት ጀኔራል ጥላሁን የሰላምታ ጥያቄ አቀረቡ “ምነው ሙሉ ቀን አንድ ጊዜም አልተገናኘንም፤ የት ጠፋህ?” አሉ ጄኔራል ተሾመ ጥያቄውን በቀጥታ በመመለስ ፋንታ፡፡
“ጄኔራል ጥላሁን “ወደ ባሕር ኃይል የገባውን ሠራዊት እያስተባበርሁ የውጊያውን ሁኔታ እየተቆጣጠርሁና ለበላይ አካል ሪፖርት ሳደርግ ነው የዋልሁት፤ አሁን ያለሁት ባሕር ኃይል መደብ ውስጥ ነው” የሚል መልስ ሰጡ፡፡
“ምነው ጥላሁን ጠላት ሬዲዮናችንን ጠልፎ ሊሰማው ይችላል፡፡ ለምን እዚህ ነው ያለሁት ብለህ ቦታህን በጦር ሜዳ ሬዲዮ ግልጽ ታደርጋለህ?” አሉ ጄኔራል ተሾመ በቁጣ፡፡
“አዎ ይቅርታ ያው ወደ ውጊያ ገብተን ስላለን ምን ምሥጢር አለ ብዬ ነው” አሉ ጄኔራል ጥላሁን፡፡
“አሁን ምን ልታዘዝ?” አሉ ጄኔራል ተሾመ፡፡
“አሁን የፈለግሁህ በዛሬው ጦርነት፣ በወገን ጦርና በጠላት ላይ የደረሰውን ዝርዝር ሪፖርት የበላይ አካል ስለሚፈልግ በተቻለ ሁኔታ ሪፖርት እንድትሰጠኝ ነው” አሉ ጄኔራል ጥላሁን፡፡
“ጄኔራል ተሾመ በጥያቄው ግልጽነት አልተደሰቱም፡፡ “ምነው ምን ሆንህ ጥላሁን? እንዲህ በግልጽ አታውራ፤ የጦር ሜዳ ሬዲዮ ጥሩ አይደለም። ጠላት እንደሚፈልግ እወቅ፡፡ ዝርዝር ሪፖርቱ በሬዲዮ ሠራተኞች በኩል በምሥጢር ኮድ ታስሮ ይላክልሃል፡፡ አሉ ጄኔራል ተሾመ፡፡ የጄኔራል ጥላሁን ትዕዛዝ በፍጹም አልጣማቸውም፡፡ አንቱ ከማለት ይልቅ አንተ እያሉ ይዘረጥጧቸው ነበር (ከገጽ 122-123)” በማለት “ሰማሁት፤ አየሁት” ያለውን የሁለቱ ጄኔራል መኮንኖች ምልልስ አስፍሯል፡፡
፶ አለቃ ታደሰ ቴሌ፤ የሁለቱን ጄኔራሎች ምልልስ ሰማሁ ያለው የካቲት 3 ቀን 1982 ዓ.ም ነው፡፡ በዕለቱም ጄነራል ተሾመ የተጠየቁትን ሪፖርት ለጄነራል ጥላሁን ሰጡ፡፡ (ታደሰ ከጄኔራል ተሾመ የማይለየው የፖለቲካ ሠራተኛ ስለሆነ መሆኑን አንዘንጋ) የካቲት 4 ቀን 1982 ዓ.ም (ሁለቱ ጄኔራሎች በሬዲዮ ከተወራረፉ በማግስቱ) ጄኔራል ጥላሁን ክፍሌ፣ ጄኔራል ዓሊ ሐጂ አብዱላህና ካፒቴን ፀጋዬ መኮንን የሰሜን ቀይ ባህር ኃይል ም/አዛዥ ባሕር ኃይል መደብ ውስጥ እያሉ በሻዕቢያ ተማረኩ፤ የጄኔራል ተሾመ ስጋትም እውነት ሆነ፡፡
ከዚህ ጋር አያይዘን ልንመዝነው የሚገባ ሌላ መረጃም በ “የቀድሞው ጦር (ገፅ 643)” ላይ እናገኛለን፡፡ ጄኔራል ጥላሁን ቀድሞውንም የመክት ዕዝ ዋና አዛዥ ሆነው ሲሾሙ፣ በጤና ምክንያት ወደ አስመራ መሄድ አለመፈለጋቸውን፤ ወደተባለው ቦታ የሄዱትም በፕሬዚዳንት መንግሥቱ ተፅዕኖ መሆኑን፣ አስመራ ከሄዱም በኋላ ህመማቸው ጠንቶ ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ አውሮፕላን ማረፊያ እያሉ ምፅዋ ላይ ውጊያ መጀመሩ ከቤተመንግሥት እንደተነገራቸውና ሄደው ማዋጋት እንዳለባቸው የፕሬዚዳንት መንግሥቱ ልዩ አማካሪ መንግሥቱ ገመቹ እንደነገሯቸው፤ ጤናዬ ታውኳል ብለው ቢናገሩም ሰሚ ማጣታቸውን፤ ረዳት ጦር ካልተሰጣቸው በዕዛቸው ስር በነበረው ሠራዊት ብቻ ተዋግተው ሻዕቢያን እንደማያሸንፉ ቢናገሩም ጆሮ ዳባ ልበስ መባላቸውን ገልጠዋል፡፡
ሆኖም ከጦርነቱ በኋላ ህክምና ይደረግላቸው፤ በሻዕቢያ ምርኮ ውስጥ ናቅፋ በረሃ ሲኖሩ በረሃው ተስማምቶአቸው ጤናቸው ይመለስ፣ ጄኔራሉ የሰጡት መረጃ በ“የቀድሞው ጦር” መጽሐፍ አልተወሳም፡፡ ወይም ስለ ጤናቸው ያነሱት ነገር የለም በሌላም በኩል የወታደራዊ ዕዝ ሰንሰለቱ የተጠበቀ አይመስልም፤ የ2ኛው አብዮታዊ ሠራዊት ዋና እና ምክትል አዛዦች ቅርባቸው (አስመራ) እያሉ እንዴት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ (ፕሬዘዳንት መንግሥቱ) ጋ ጉዳዩ ደረሰ? የሻዕቢያን እንቅስቃሴ የመቆጣጠር ኃላፊነት የፕሬዚዳንቱ ነው ወይስ በየግንባሩ የተሰለፈው አብዮታዊ ሠራዊትና አዛዦች? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡
በ “የቀድሞው ጦር” መጽሐፍ (ገፅ 643) ላይ “በምፅዋ ግንባር ጦርነት መከፈቱን የሰማሁት ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ አውሮፕላን ማረፊያ ሳለሁ ነው“ ብለው ጄኔል ጥላሁን የሰጡትን መረጃ፣ ከ፶ አለቃ ታደሰ ቴሌ ሳልቫኖ ጋር መጋቢት 19 ቀን 1985 ዓ.ም ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤  “አይ ምፅዋ (ገፅ 265)”  ላይ ሻዕቢያ ጥቃት መክፈቱን የሰሙት ከሌሊቱ 10፡00 የ606ኛ ዘመቻ መምሪያ መኮንን ስልክ ደውሎ ከሌሊቱ 8፡30 ሰዓት ገደማ በሰለሞና እና አዲሹማ ግንባር ባለው የ6ኛ ክ/ጦር ዋና ተከላካይ ኃይል ላይ ሻዕቢያ ጥቃት መሰንዘሩን ነገረኝ” ብለዋል፡፡ ጄኔራል ጥላሁን በአንድ ጉዳይ ላይ ለሁለቱ ጸሐፊዎች ከሰጧቸው ሁለት ሃሳቦች የቱን እንመን?
በሌላም በኩል የቀድሞው ጦር (ገፅ 637) ላይ በምፅዋ ግንባር ሻዕቢያ ጥቃት ሊሰነዝር እንደሚችል የደረሰ መረጃ ስለነበረ የ606ኛ ኮር አዛዥ፣ የ6ኛ ነበልባል ክ/ጦር አዛዥ፣ የአየር ኃይል የሰሜን መደብ አዛዥ፣ እና የባሕር ኃይል ሰሜን ቀይ ባሕር መደብ አዛዥ ያሉበት የሕብረት ዕዝ ተቋቁሞ እንደነበር ይነግረናል፡፡ የዕዙ መቋቋም ሶስቱን ኃይሎች ያስተባበረ ውጊያ ለማካሄድ እንዲረዳ ታስቦ ነው፤ የኅብረት ዕዙ አስተባባሪ ደግሞ ብ/ጄኔራል ጥላሁን ክፍሌ ነበሩ፤ ግን የዕዙን መሪነት ተግባራዊ ስላላደረጉት ዕዙ ከሰመ፤ ይህንንም አንዳንድ ወገኖች “ቀድሞውንም ብ/ጄኔራል ጥላሁን ከሻዕቢያ ጋር የመዋጋት ፍላጎት አልነበራቸውም” እንዲሉ ሁኔታው የተመቻቸ ይመስላል፡፡
በአጠቃላይ የምፅዋ ውድቀት በተነሳ ቁጥር የዕዙ ዋና አዛዥ የብ/ጄኔራል ጥላሁን ክፍሌ ስም መነሳቱ ስለማይቀር፣ ያለፈው መንግሥትና የጦር ሜዳ አለቆቻቸው እሳቸውን አስመልክተው የሰጧቸው መግለጫዎች፣ ራሳቸው ጄኔራሉ “ስሜ ጐድፏል፣ ለሀገሬ የሚገባኝን ወታደራዊ ተግባር የፈፀምሁ ሰው ነኝ” ሲሉ የሰጧቸውን ማስተባበያዎች፤ በ1981 መፈንቅለ መንግስት ውስጥ ነበርኩበት (አይ ምፅዋ ገፅ 238)” ብለው የሻዕቢያ ማዕከላዊ ኮሚቴ ዋና ጽ/ቤት በነበረው አንደርበብ ዋሻ ውስጥ ከብ/ጄኔራል ዓሊ ሐጂ አብዱላህ ጋር የተጨዋወቱትን፣ ለገስጥ ተጫነ ነግረውት በ”የቀድሞው ጦር” መጽሐፍ ውስጥ የሰፈረውን፣ ወዘተ አመዛዝነው ትክክለኛውን መረጃ ቢሰጡን ስለ እርስዎ ሀቁን ልናውቅና በነሲብ ከመፈረጅ ልንድን እንችላለን፡፡ በወቅቱ በምፅዋ ግንባር የነበሩና በህይወት ያሉ የሰራዊቱ አባላትም ከህሊና ዕዳ ነፃ ይወጣሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡
በተረፈ በነበራቸው የሥልጣን ፍላጐት ወይም ፕሬዚዳንት መንግሥቱን በመጥላት፤ ወይም ከወኔ ቢስነት በተነሳ ምክንያት አለዚያም በአፍቅሮ ሴት ከአስመራ ቆነጃጅት ጋር ቀሚስ ሲጋፈፉ ምስጢራቸውንም ገመናቸውንም አጋልጠው የሚመሩትን ሠራዊት ለሻዕቢያ እሳት ዳርገውት፣ አገሪቱንም ከውርደት ላይ የጣሉ አንዳንድ ጄኔራሎች የጐደፈና ያደፈ ስማቸውን ያደሱ መስሏቸው ግለታሪካቸውን እየጻፉ ወይም እያስጻፉ፣ ራሳቸውን ቅዱስና የጀግኖች ጀግና አድርገው ለማቅረብ ሲሞክሩ በተደጋጋሚ አይተናል፡፡ ከዚህ በተለየ መልኩ የቀድሞው ጦር መጽሐፍ አዘጋጅ ኮሚቴውና ጸሐፊው ገስጥ ተጫኔ፤ የራሳቸውን ሳይሆን የመላ ሠራዊቱን (ምሉዕ ነው ብዬ ባላምንም) ታሪክ ለመጻፍ ያደረጉት ጥረት በእጅጉ የሚደነቅ ነው፡፡

Published in ጥበብ

የሰዓሊው ሐውልት እስካሁን አልተሰራም

ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ ሁለተኛ ዓመታቸውን ቢያስቆጥሩም በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የሚገኘው መቃብራቸው እስካሁን ሐውልት አልተሰራለትም። እኛ ግን የሜትር አርቲስት ሎሬት አፈወርቅ ተክሌን ሁለተኛ ሙት ዓመት ለመዘከር አርቲስቱ ከማለፋቸው ከ25 ዓመት በፊት የታተመውን “አፈወርቅ ተክሌ፤ አጭር የሕይወት ታሪኩና ምርጥ ሥዕሎቹ” የተሰኘ መጽሐፍ ለመቃኘት እንሞክራለን።
በመፅሃፉ የመጀመሪያው ምዕራፍ ላይ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት የአርቲስቱን የትውልድ፣ የትምህርትና የሥራ ታሪክ በዝርዝር አቅርበዋል። በርካታ ሥዕሎች፣ ፎቶግራፎችና ደብዳቤዎችን በማካተት በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች የተዘጋጀው መጽሐፍ፤ ከያዛቸው ቁምነገሮች ጥቂቱን እነሆ:-
የሲልቪያ ፓንክረስት ውለታ
ሲልቪያ ፓንክረስት፤ በሥነ ጥበብ በትምህርት የዳበረ ዕውቀት ቢኖራቸውም ለሴቶች መብት መከበርና የፋሽስት ኢጣሊያን ወረራ ለመመከት ከኢትዮጵያ አርበኞች ጎን ቆመው ሲታገሉ ስለነበር በሙያው አልገፉበትም፡፡ የሙያውን ሰዎች ግን ሲረዱ ነው የኖሩት፡፡ የሲልቪያ ፓንክረስትን እገዛ ካገኙ የሥነጥበብ ባለሙያዎች መካከልም ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ አንዱ ነበሩ፡፡
ሲልቪያ በኮተቤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጉብኝት ሲያደርጉ ነበር አፈወርቅ ተክሌ በደብተር ላይ የሳላቸውን ሥዕሎች አይተው የተደነቁት፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ታዳጊውን ያግዙትና ይደግፉት ጀመር፡፡ ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ ይሄን አስመልክቶ በሰጡት ምስክርነት፤ “ሚስ ፓንክረስት ሁለተኛ የመንፈስ እናቴ፣ መካሪዬ፣ አስተማሪዬና በተለይ ስለጥበቤ ከፍተኛ እንዲሁም ኃይለኛ ሂሰኛዬ ነበሩ። ከዚህም በላይ ለሀገሬና ለሰው ልጅ ከፍተኛ ፍቅር እንዲኖረኝ፤ በስራዬ ተደናቂ ውጤትን በማገኝበት ጊዜ ከመኩራራት በጥብቅ እንድቆጠብና መሥራት፣ መሥራት፣ አሁንም መሥራት እንዳለብኝ እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ ጎትጓቼ ነበሩ፡፡” ብለዋል - በመፅሃፉ ውስጥ፡፡
ጥቅምት 12 ቀን 1925 ዓ.ም በአንኮበር ከተማ የተወለዱት ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ፤ ከልጅነታቸው አንስቶ በፍቅር የወደቁለትን የሥዕል ጥበብ፤ በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶችም ገፍተውበት፣ ወደ እንግሊዝ ምህንድስና እንዲማሩ ሲላኩም ሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት በመግባት ፍላጎታቸውን በዕውቀት ካዳበሩ በኋላ፣ ወደ አገራቸው የተመለሱ ሲሆን፤ በ1947 ዓ.ም በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት አዳራሽ የሥዕል ኤግዚቢሽን አቅርበው ብዙዎችን አስደመሙ፡፡
ይህንን የተመለከቱት ንጉሥ አፄ ኃይለሥላሴ፤ አርቲስቱ ወደ ጣሊያን፣ ፈረንሳይ፣ ስፔን፣ እንግሊዝ፣ ፖርቹጋል፣ ግሪክ እና ሌሎች አገራት ሄደው እዚያ የሚገኙ የኢትዮጵያ ብራናና ሥዕላዊ ሥራዎችን ለሁለት ዓመት እንዲያጠኑ ድጋፍ አድርገውላቸዋል። ይሄም የንጉሡ መንግሥት ለሥነ ጥበብ ሙያና ባለሙያ ትልቅ ቦታ ይሰጥ እንደነበር አመላካች ነው።
በመፅሃፉ ውስጥ ከተካተቱት የሥነ - ጥበብ ሥራዎች መካከል የአርቲስቱ የሥዕል ንድፎች፣ የቀለም ቅቦች፣ ሞዛይኮች፣ የመስታወት ቅብ ሥዕሎች፣ ቅርፃ ቅርፆች፣ የቴምብር ሥራዎች፣ በመጫወቻ ካርታ የተሰሩ ሥዕሎችና ፖስተሮች ይገኙበታል፡፡ ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽና ሌሎች ቦታዎች ታላላቅ የሥነጥበብ ሥራዎችን ሲሰሩ ኢትዮጵያዊያንን ብቻ ሳይሆን የፈረንሳይና ሌሎች የውጭ አገር ዜጎችን በረዳትነት ይቀጥሩ እንደነበር መፅሃፉ በፎቶግራፍ አስደግፎ ይገልፃል፡፡
ለሥዕሎቻቸው ሞዴል ሆነው ያገለገሉ ሰዎችን ፎቶግራፎችም አካትቷል መፅሃፉ፡፡ የአንዳንዶቹን እስከነማንነታቸውም ጭምር ያስተዋውቃል፡፡ ለኢትዮጵያዊት ሴት ሥራቸው ሞዴል የሆነችው የሮም ነዋሪ አንዷ ናት፡፡ አለቃ ለማ ሌላኛው ናቸው። “ለእናት ኢትዮጵያ” ስዕል ሞዴል የሆነችው ሴት እንዲሁም “ፀደይ” በሚል ርዕስ ለሚታወቀው “ኢትዮጵያዊት ወ/ሮ” ሥራቸው ሞዴል የሆኗቸው እንስቶች ፎቶግራፍ ቀርቧል፡፡
የብሔራዊ ክብረ በዓል ልብሶች ንድፍ
“አፈወርቅ ተክሌ አጭር የሕይወት ታሪኩና ምርጥ ሥዕሎቹ” በተሰኘው መጽሐፍ ውስጥ ከተካተቱት የመግለጫ ስዕሎች መካከል አርቲስቱ ጥናት ያደረጉባቸውና ጥናቱ እንዴት እንደተካሄደ የሚያስቃኙ ይገኙበታል፡፡ በእስክርቢቶ፣ በእርሳስ፣ በጠመኔ፣ በአንድ ቀለም…ወዘተ ጥናት ከተሰራባቸው ርዕሰ ጉዳዮች መካከል አርበኛ፣ “ፕሬዚዳንት ክዋሜ ንክሩማ፣ ባህላዊ የእጅ ሥራ፣ የድርቁ ሰቆቃ፣ ለበገና ቅኝት፣ የአፍሪካ አንድነት ባንዲራ…” የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
“አፍሪካዊያን ላደረጉት የነፃነት ትግል አፈወርቅ በጥበብ ሥራዎቹ አግዟል፡፡ ለአፍሪካ አንድነት ዓርማና ባንዲራም አያሌ ጥናቶችን ካደረገ በኋላ፣ ከአሥር በላይ ንድፎችን ሰርቶ አውጥቷል” ይላል - መጽሐፉ፡፡
የኢትዮጵያውያን የአገር ባህል አልባሳትን በተመለከተም በአርቲስቱ የተሰራውን ንድፍ “ሰዓሊው በማዕረግና የሽልማት ልብሶቹ” በሚል ፎቶግራፍ ቀርቧል፡፡
“ሥርዓተ ቅዳሴ፣ የሂሳብ ተማሪው፣ ዝናብ ያዘለ ደመና፣ ጫማ ጠራጊዎች በአዲስ አበባ፣ የተሰበረው ጀበና፣ ሻምላ ተጫዋቾች፣ እንቁላል ቤት፣ ጥንታዊ ሮማ፣ የወይፈን ውጊያ፣ ጉግስ ጨዋታ፣ የጦርነት ሰቆቃ፣ ደመራ፣ የመስቀል አበባ፣ ነርሷና ሕመምተኛው፣ ሚሊሺያ፣ የታመሙና የተራቡ…” የተሰኙ በርካታ ሥዕሎችን የያዘው መጽሐፉ፤ እስከ 1979 ዓ.ም ድረስ ያሉትን የሰዓሊውን ሥራዎች ብቻ ያካተተ መሆኑ ሲታሰብ በእጅጉ ያስደንቃል፡፡
ከ1979 እስከ 2004 ዓ.ም ባሉት 25 ዓመታት ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ የሰሯቸው ሥዕሎች ብዛትና አይነት በእጅጉ ማጊጓቱ አይቀርም፡፡  የአርቲስቱን ሙሉ የሕይወትና የሥራ ታሪክ በመጽሐፍ ሰንዶ ለሕዝብ ማቅረብ የግድ ነው፡፡ ቪላ አልፋ ሳይከፈት፣ የባለታሪኩም ሐውልት ሳይሰራ ሁለት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የአርቲስቱ አድናቂዎች ጥያቄና ምኞት ምላሽ የሚያገኘው መቼ ይሆን?
“አፈወርቅ ተክሌ፡ አጭር የሕይወት ታሪኩና ምርጥ ሥዕሎቹ” የተሰኘው መጽሐፍ ለጊዜው እንደ ሐውልት መታሰቢያ ሆኖ፤ የአርቲስቱን ሁለተኛ ሙት ዓመት ለመዘከር ስለረዳን፣ በመጽሀፉ ዝግጅትና ሕትመት ሥራ ላይ የተሳተፉትን ሁሉ ልናመሰግን እንወዳለን፡፡

Published in ጥበብ
Monday, 14 April 2014 09:59

የቀልድ - ጥግ

አንድ ባለመደብር ሰውዬ ወደ ሁሉን - አዋቂ ነኝ ባይ (Know it all) ወዳጁ ጋ ሄዶ፤
“ጠዋት ጠዋት ስነሳ ጤና አይሰማኝም፡፡ የዞረ-ምድር እንዳለበት ሰው ጥውልውል ያደርገኛል” አለው።
ሁሉን አዋቂው ሰውም፤ “ማታ ስትተኛ ወተት ጠጣ” አለው፡፡
ባለመደብሩ፤ “እኔማ በየማታው ወተት ሳልጠጣ አድሬ አላውቅም”
ሁሉን አዋቂነኝ - ባዩም፤ ወዲያው እጥፍ አለና፤ “ይሄውልህ ዋናው ችግርህ እሱ ነው፡፡”
“እንዴት”
“ቆይ ላስረዳህ፡፡ አየህ ወተቱን ትጠጣና አልጋህ ላይ ትወጣለህ ከዚያ ከግራ ወደቀኝ ትገላበጣለህ። ስትገላበጥ ወተቱ አይብ ያወጣል። ደሞ ስትገላበጥ ስትናጥ አይቡ ደግሞ ቅቤ ይወጣዋል፡፡ ከዛ ቅቤው ወደ ስብነት ይለወጣል። ስቡ ደወ ስኳርነት ይለወጣል። ቀጥሎ ስኳሩ ወደ አልኮልነት ይቀየራል። ስለዚህ ጠዋት ስትነሳ የዞረ-ምድር ናላህን ያዞረዋል። ለዚህ ነው የሚያጥወለውልህ!” አለና አብራራለት፡፡
*       *       *
አንድ ባለመደብር ሰውዬ ወደ ሁሉን - አዋቂ ነኝ ባይ (Know it all) ወዳጁ ጋ ሄዶ፤
“ጠዋት ጠዋት ስነሳ ጤና አይሰማኝም፡፡ የዞረ-ድምር እንዳለበት ሰው ጥውልውል ያደርገኛል” አለው።
ሁሉን አዋቂው ሰውም፤ “ማታ ስትተኛ ወተት ጠጣ” አለው፡፡
ባለመደብሩ፤ “እኔማ በየማታው ወተት ሳልጠጣ አድሬ አላውቅም”
ሁሉን አዋቂነኝ - ባዩም፤ ወዲያው እጥፍ አለና፤ “ይሄውልህ ዋናው ችግርህ እሱ ነው፡፡”
“እንዴት”
“ቆይ ላስረዳህ፡፡ አየህ ወተቱን ትጠጣና አልጋህ ላይ ትወጣለህ ከዚያ ከግራ ወደቀኝ ትገላበጣለህ። ስትገላበጥ ወተቱ አይብ ያወጣል፡፡ ደሞ ስትገላበጥ ስትናጥ አይቡ ደግሞ ቅቤ ይወጣዋል፡፡ ከዛ ቅቤው ወደ ስብነት ይለወጣል፡፡ ስቡ ደወ ስኳርነት ይለወጣል። ቀጥሎ ስኳሩ ወደ አልኮልነት ይቀየራል። ስለዚህ ጠዋት ስትነሳ የዞረ-ምድር ናላህን ያዞረዋል። ለዚህ ነው የሚያጥወለውልህ!” አለና አብራራለት፡፡

Published in የግጥም ጥግ

የታላቁ የህዳሴ ግድብ
የስራ ድባብ-  በሰራተኞች አንደበት

አቶ ተመስገን አበበ ይባላሉ፡፡ ከሰሜን ጎጃም አጨፈር ወረዳ፣ ከጣና በለስ አካባቢ እንደመጡ ይናገራሉ፡፡ የህዳሴው ግድብ አካባቢ ያለው መሸጋገሪያ ድልድይ ሳይሰራ በፊት ሰዎችን በጀልባ በማሻገር ነበር የመተዳደሪያ ገቢያቸውን የሚያገኙት። ቦታው ለግድቡ መስሪያ በጂኦሎጂስቶች ሲጠና እሳቸው ሰዎችን በጀልባ ያሻግሩ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ጥናቱ ተጠናቆ ስራ ሲጀመር የህዳሴውን ግድብ ተቀላቀሉ፡፡ በመጀመሪያ በጉልበት ሰራተኝነት ተቀጥረው ሰሩ፡፡ ከዚያም ቀስ በቀስ በጥረታቸው ረዳት የክሬን ኦፕሬተር ለመሆን በቁ፡፡ አሁን ዋና የክሬን ኦፕሬተር በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡
የህዳሴው ግድብ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበት ሶስተኛ ዓመት ክብረ በዓል ዕለት እሳቸው ሲሰሩ ነው ያደሩት፡፡ ቢሆንም የመኝታቸውን ሰዓት ሰውተው፣ የክት ልብሳቸውን ለብሰው ለበዓሉ በተደኮነው ድንኳን ውስጥ ተገኙ፡፡
የሚገርመው ደግሞ የ23 ዓመት ዕድሜ ያለው የመጀመሪያ ልጃቸውም እዚያው ነው የሚሰራው። በሜካኒክነት “በዓሉን ማክበር አለብኝ ብዬ እንጂ አሁን የመኝታ ሰዓቴ ነበር፤ ሌሊት ተረኛ ስለነበርኩ” አሉኝ አቶ አበበ፡፡ ታዲያ ስራ እንዴት ነው አልኳቸው፡፡ “ስራውም ክፍያውም ጥሩ ነው፤ ብቻ ሙቀቱ አስቸጋሪ ነው፤ እሱንም ቢሆን አሁን እየለመድነው ረስተነዋል” ሲሉ መለሱልኝ። የምግብ፣ የጤናና የእንቅልፍ ሁኔታን የተመለከቱ ጥያቄዎች አነሳሁ፡፡ አብዛኛው ሰራተኛ በየመኝታ ክፍሉ አብስሎ ነው የሚበላው፡፡ ለምን ቢባል? በሬስቶራንቱ የሚሸጠው ምግብ ውድ ነው ይላሉ። የጤና ሁኔታ እዚያው  ህክምና ስለሚያገኙ እንደማያሳስባቸው የተናገሩት አቶ አበበ፤ “ወባም ብትሆን በሁለት ክኒና ድራሿ ይጠፋል” በማለት ፈገግ አሰኙኝ፡፡
ወጥ ራሳቸው ሰርተው እንጀራ “ባምዛ” ከተሰኘ ከተማ በኮንትራት እንደሚያስመጡ የገለፁልኝ ክሬን ኦፕሬተሩ፤ ምግብ ማብሰሉ ትንሽ ጊዜያቸውን እንደሚሻማቸው ይናገራሉ፡፡ በተረፈ ስራው ሌትም ቀንም በትጋት እየተሰራ እንደሆነና የዚህ ስራ አካል መሆናቸው ደስተኛ እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል፡፡
ከሰሜን ጎንደር ከደልቂ አካባቢ እንደመጣች የምትናገረው የ22 ዓመቷ አብነት አዋዝ፤ በመኪናና በግቢ ደህንነት ስራ ላይ ከተሰማራች ሁለት ዓመት አስቆጥራለች፡፡ በአጠቃላይ በስራው ደስተኛ ነኝ የምትለው ወጣቷ፤ “በዚህ ግድብ ስራ ላይ የሚሰሩት ሁሉ ደሞዛቸው ቢለያይም ስራውን ግን ሁሉም እኩል ይሰራሉ” ብላለች፡፡ ሁሉም በየዘርፉ በንቃትና በትጋት ስለሚሰራ ደስ ይላል፤ የመኝታው ደረጃ፣ የምግቡ አይነትና ደሞዙ ግን ልዩነት አለው ያለችው አብነት፤ በመኝታ በኩል ለስምንት ሰዎች፣ ለአራት ሰዎች፤ ለሶስት ሰዎና ለሁለት የሚሰጥ የመኝታ ክፍል እንዳለ ጠቁማ ይህም እንደየስራ ደረጃቸው የተመደበ መሆኑን ትናገራለች፡፡ መኝታው ኤሲ (የአየር ማቀዝቀዣ) ያለውና የሌለው እንደየደረጃው የተከፋፈለ መሆኑን የምትገልፀው ወጣቷ፤ ያም ሆኖ ሰራተኛው ግድቡን በማሰብ ሳይለግም እየሰራ ነው ብላለች፡፡”
ሻምበል ታደሰ ረጋሳ ይባላሉ፡፡ ትውልድና እድገታቸው ጅማ ነው፡፡ በህዳሴው ግድብ በጥበቃ ስራ ላይ ከተሰማሩ አንድ ዓመት እንደሆናቸው ይናገራሉ፡፡ በስራ ላይ የሙቀቱ ከፍተኛነትና  ውሃ ጥሙ ካልሆነ በስተቀር ሌላ ችግር እንደሌለ ገልፀው፣ ስራቸውን በአግባቡ እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል። በስራው ላይ ከእለት እለት ለውጥና ግስጋሴ እያስተዋሉ መሆናቸው እንደሚያስደስታቸው ሻምበል ታደሰ፤ ወደ ግድቡ ስራ የመጡ ሰሞን ፀሐዩና ውሃ ጥሙ ፈትኗቸው እንደነበር ይናገራሉ። “ሆኖም በስራ ባልደረቦቼ ማበረታቻና አይዞህ ባይነት አሁን ሁሉንም ተላምጄው በንቃት እየሰራሁ ነው” ብለዋል፡፡
የ28 ዓመቱ ወጣት ስሙን መጥቀስ አልፈልገም። ወደ ህዳሴው ግድብ በጉልበት ሰራተኝነት የሄደው ከሁለት ዓመት በፊት ከጎጃም ሉማሜ ከተባለ ቦታ እንደሆነ ይናገራል፡፡ በአካባቢው አባቱን በእርሻ እያገዘ ትምህርቱን ጎን ለጎን በመከታተል እስከ 10ኛ ክፍል መዝለቁን አጫውቶኛል፡፡ አባቱ እድሜ እየተጫናቸው ሲመጣ፣ ኃላፊነቱ እሱ ላይ ስለወደቀ፣ ትምህርቱን ከ10ኛ ክፍል በላይ መቀጠል አልቻለም። በአካባቢው ወግና ባህል መሰረት ትዳር ቢይዝም አባቱ ቆርሰው የሰጡት መሬት ኑሮውን የሚያሻሽል ሆኖ ስላላገኘው፣ ወደ ህዳሴው ግድብ በጉልበት ሰራተኝነት ለመሰማራት መሄዱን ይናገራል፡፡
“ከሙቀቱ ጋር የጉልበት ስራ ይከብዳል፤ በማሽን እየታገዙ መስራትና የጉልበት ስራ ይለያያል” የሚለው ወጣቱ፤ ከሁሉም በላይ በጉልበታቸው የሚሰሩ ሰራተኞች ሊደነቁ እንደሚገባ በአፅንኦት ይናገራል፡፡ “ለተማረና እውቀት ላለው ሰው ስራው አይከብድም፤ ብዙ ደሞዝ ያገኛሉ፤ የሚንቀሳቀሱት በመኪና ነው፤ መኖሪያቸው የሙቀት ማቀዝቀዣ አለው” ይላል፡፡ በስራውና በአባይ ግድብ ደስተኛ እንደሆነ የሚናገረው ወጣቱ፤ “የጉልበት ሰራተኛው ሲሰራ ውሎ ወደ ማረፊያው ሲሄድ ሙቀት ይቀበለዋል፤ የተወሰነ የአየር ማቀዝቀዣ ቢኖር በደንብ አርፎ ጉልበት ለመሰብሰብና ነገ የበለጠ ለመስራት ያግዝ ነበር” በማለት ለጉልበት ሰራተኛው ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ያሳስባል፡፡
“ይህን የምነግርሽ በስራው ደስተኛ አይደለሁም ተበድያለሁ ለማለት ሳይሆን ስራው የጉልበት ስራ በመሆኑ በምግብና በማረፊያ በኩል የተሻለ ነገር ካላገኘሽ ለነገ ስራ ለመዘጋጀት ይከብዳል ለማለት ነው” ያለው ወጣቱ፤ እንደዚያም ሆኖ ሁሉም በየፊናው ስራውን በአግባቡ እየሰራ ስለመሆኑ እማኝነቱን ሰጥቷል፡፡   
መጋቢት 24 ቀን 2006 ዓ.ም ነበር የህዳሴው ግድብ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበት ሶስተኛ ዓመት ክብረ በዓል የተከበረው፡፡ በእለቱም ም/ጠቅላይ ሚኒስትርና የህዳሴው ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ጽ/ቤት ብሔራዊ ም/ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ደመቀ መኮንንን ጨምሮ በርካታ የመንግስት ባለሥልጣናትና የሳሊኒ ኮንስትራክሽን ኃላፊዎች የግድቡን ሂደትና የደረሰበትን ደረጃ አስመልክተው ንግግር አድርገዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አንጋፋውን ድምፃዊ ነዋይ ደበበን ጨምሮ ሌሎችም በስፍራው ተገኝተው በግድቡ ዙሪያ ያቀነቀኑ ሲሆን፣ የተለያዩ ግጥሞችም ቀርበዋል፡፡
ጉዞ በጀመረ በሶስተኛው ቀን ጉባ የደረሰው የጋዜጠኛ ቡድን በራሱ ጥረት ተዘዋውሮ ነገሮችን ለማየት ሙከራ ከማድረጉ በስተቀር የተዘጋጀለት የጉብኝት ፕሮግራም አልነበረም፡፡ በእርግጥ በዓሉ እየተከበረም ስራ አልተቋረጠም፡፡ ተራራ የሚንደው ማሽን ተራራ ይንዳል፡፡ በድማሚት የሚፈርሰውም ይፈርሳል፣ የኮንክሪት ሙሌቱ ይካሄዳል፣ ሆደ ሰፊዎቹ አፈርና አሸዋ አመላላሽ መኪኖች እንደጉንዳን ይርመሰመሱ ነበር፡፡
በዓሉ እየተከበረ አንድ ድማሚት ፈነዳ፡፡ የእለቱ የመድረክ መሪዎች ከነበሩበት አንዷ አርቲስት ሜሮን ጌትነት “አሁን በስራ ላይ ያለው ድማሚት ሲፈነዳ፣ ለበዓል እንደሚተኮስ መድፍ ቁጠሩት” በማለት ተናገረች፡፡ ድማሚቱ አካባቢውን አናጋው፣ ጉሙን እያትጎለጎለና እያሰፋ ወደ ሰማይ ወጣ፡፡ ስራው በዚህ መንገድ ቀጥሏል፡፡ በቅርብ ሆኖ ስራውን ለማየት ለበዓሉ የተጣለው ድንኳን ኮንክሪቱ ከሚሞላበት ቦታ ይርቃል፡፡
በዚያ ላይ በዓሉ እየተከበረ በነበረበት ወቅት ሙቀቱ ከ48-49 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ደርሶ ስለነበር፣ በእግር ተዘዋውሮ ለመጎብኘት አዳጋች ነበር፡፡ በስፍራው በዓሉን በካሜራቸው እየቀረፁ የነበሩ አንድ የፎቶግራፍ ባለሙያ በሙቀቱ ሩሃቸውን ስተው ወድቀዋል፡፡
በእለቱ ከተጋበዙት አርቲስቶች አንዱ ደምሴ ዋኖስ፤ “አዲስ አበባ በ28 ድግሪ ሴንቲ ግሬድ ነበር የምዘፍነው፤ አሁን በ42 ድግሪ ሴንቲግሬድ ነው” በማለት ሲቀልድ፣ ሠራተኞች እቺን ተቀብለው “የሙቀቱ መጠን ተጭበርብሯል፤ 490C ገብቷል እኮ” ሲሉ አስተባበሉ፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ በዓሉ ወደ መጠናቀቁ ሲቀርብ፣ “የሳሊኒ አርማ ያለበት ማንጠልጠያ ያለው ባጅ ያደረጋችሁ እንግዶች እባካችሁ ወደ ተዘጋጁት ቢሾፍቱ አውቶብሶች ግቡ” ተባለ፡፡ በአንገት ላይ ባጅ ያደረገ ጋዜጠኛ የለም፤ እንግዶች ወደ አውቶብሱ የገቡት የመስክ ጉብኝት ለማድረግ ነው፤ ጉብኝቱ ጋዜጠኞችን ያገለለበት ምክንያት ባይታወቅም አስገርሞናል፡፡
በነጋታው አሶሳ ባምቡ ሆቴል ግቢ ውስጥ ለ25 ደቂቃ ገለፃ ያደረጉት የህዳሴው ግድብ ፕሮጀክት ማናጀር ኢ/ር ስመኘው፤ “በትላንትናው እለት ልጁን እንደሚድር አባት ሆኜ ሁሉንም ማስተናገድ አልቻልኩም፤ ይቅርታ አድርጉልኝ” በማለት ነው ንግግራቸውን የጀመሩት፡፡
“አሁን የተለየ ዘመን ላይ ነው ያለነው፤ ጥላቻን ቅያሜን፣ ዘርን፣ ሀይማኖትን ማዕከል ያላደረገ አገራዊ ፋይዳ ያለው ስራ እየተሰራ በመሆኑ የሚዲያው ሚና ትልቅ ነው፤ አቅማችን ናችሁ” አሉ፡፡ “የዚህ የተለየ ዘመን አካል በመሆናችሁ ስለመጣችሁ ደስ ብሎናል። ስትዘግቡም ግብፅ የምትለውን እረስታችሁ ስለግድቡ የምታውቁትንና ያያችሁትን በትክክል መረጃ አቅርቡ” ሲሉም ምክራቸውን ለገሱ፡፡
“ለምሳሌ ግብፅ የግድቡ ቁመት ወደ ዘጠና ሜትር ዝቅ ይበል ትላለች፤ እናንተ ግን 145 ሜትር ቁመት እንደሚኖረው እንጂ የግብፅን ድምፅ ማስተጋባት የለባችሁም” በማለት አከሉ፡፡
ታላቁ የህዳሴ ግድብን በጊነስ ቡክ ኦፍ ሪከርድስ ለማስመዝገብ ንቅናቄ እንደሚጀመር ኢ/ር ስመኘው በንግግራቸው ገልፀዋል፡፡ ግድቡ ሲጠናቀቅ 246 ኪ.ሜትር ውሃው ወደ ኋላ እንደሚተኛ፣ ውሃው የሚተኛው 1874 ስኩየር ኪሎ ሜትር ላይ እንደሆነ፣ 74 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሀ እንደሚይዝ፣ 59 ቢሊዮን ኪዩቡ ለኃይል ማመንጨነት ሲውል ቀሪው በተጠባባቂ ክምችትነት እንደሚውል ኢ/ር ስመኘው የገለፁ ሲሆን ግድቡ በውሀ ምርምር ትልቅ ማዕከል እንደሚሆን፣ ለቱሪስት ፍሰትና ለእንስሳት ማርቢያነት እንደሚውል እንዲሁም በጎርፍ መጥለቅለቅ ቀርቶ ሰላማዊ የውሃ ፍሰት እንደሚኖር አብራርተዋል። የህዳሴው ግድብ አራተኛ አመቱን ሲያከብር 750 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምርም ተገልጿል፡፡ በአሁኑ ሰዓት የግድቡ ስራ 30 በመቶ መጠናቀቁም ተገልጿል፡፡


Published in ህብረተሰብ

በምዕራቡ ዓለም ለአርቲስቶችና ለዝነኞች አልባሳትንና መጫሚያዎችን በትዕዛዝ የሚሰሩ ባለሙያዎች (ዲዛይነሮች) ታዋቂዎች ናቸው፡፡ ታዋቂዎች ብቻ ሳይሆን ሃብታሞችም አንደሆኑ ይነገራል፡፡ በአገራችን በተለይ ለአርቲስቶች የሚጠበቡ ባለሙያዎችን እምብዛም አናውቅም፡፡
የተለያዩ ጫማዎችን በትዕዛዝ የሚሰራው ቸርነት - ግን ለዕውቅ አርቲስቶች በስማቸው ጫማ እንደሚሰራ ይናገራል፡፡ ከአርቲስቶችም በተጨማሪ ትላልቅ ባለስልጣናትም ደንበኞቹ ናቸው። በልጅነቱ የጥበብ ፍቅር የነበረው ቢሆንም አርቲስት መሆን እንዳልቻለ የሚናገረው ቸርነት መንገሻ፤ በሁለተኛ ደረጃ በፍቅር ወደሚወደው የጫማ ስራ ሙያ እንደገባ ይናገራል። አርቲስትነት ባይሳካለትም ለአርቲስቶች መስራት ችሏል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው ከጫማ ባለሙያው ቸርነት ጋር በህይወቱና በሙያው ዙርያ እንዲህ አውግታለች፡፡

የልጅነት ህልምህ ምን ነበር?
በልጅነቴ ብዙ መሆን የምፈልጋቸው ነገሮች ነበሩ፡፡ ከነዚያም ውስጥ አንዱ አርቲስቶችን በቅርበት ማወቅ ነበር፡፡ ቲያትር ተምሬያለሁ - ተስፋዬ አበበ እና ሽመልስ አበራ ዘንድ፡፡ ማክሲኮጊ የተባለ የቲያትር ትምህርት ቤት ገብቼም ቲያትር አጥኝቻለሁ፡፡ ከሙዚቃ መሳሪያም ኪቦርድ ተምሬያለሁ፡፡ ሆኖም አርቲስት መሆን አልቻልኩም፡፡ ከዚያ ቀጥሎ የጫማ ስራን በፍቅር ነበር የምወደው፡፡ በመሀል የእንጨት ስራም ሞክሬያለሁ፡፡
የጫማ ስራ በስንት ዓመትህ ጀመርክ?
በ12 ዓመቴ፡፡ በጫማ ስራ ውስጥ አዘጋጅ የሚባል አለ፡፡ አንዱን ቆዳ ከሌላው ቆዳ፣ ዋናውን ቆዳ ከገበሩ ጋር አጣብቆ ለሰፊው የሚሰጥ ነው፡፡ የእኔ የስራ ድርሻ አዘጋጅ ነበር፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ ቴክኒክ ነገር እወድ ነበር፡፡ ቤተሰቦቼ ይሄን ያውቁ ስለነበር ነው ከትምህርቴ ጐን ለጐን የጫማ ስራን እንዳሳድገው የፈቀዱልኝ፡፡ አንድ በቀለ የሚባል ጎረቤታችን ሃብተጊዮርጊስ ድልድይ አካባቢ በሚገኝ ጫማ ቤት ይሰራ ነበር፡፡ እዚያ ይዞኝ እየሄደ የሚያዙኝን ነገር እሰራ ነበር፡፡ እቃ ከማቀበል ጀምሮ ማለት ነው፡፡ እንዲህ ነው ስራውን የጀመርኩት፡፡
ክፍያ ነበረው?
የሳሙና በ15 ቀን 8 ብር ይሰጠኝ ነበር። በጣም ብዙ ነበር ለእኔ፡፡ ግን ለገንዘቡ ሳይሆን ስራውን በፍቅር ነበር የምወደው፡፡ እዛ ቤት ወደ ሁለት ዓመት ያህል ሰራሁ፡፡ አዲሱ ገበያ አካባቢ አሰግድ አድማሱ የሚባል ሰው፣ የአካል ጉዳተኞችን ጫማ ይሠራ ነበር፡፡ የታላቅ ወንድሜ ጓደኛ ነው። እሱ ጋ ቁጭ ብዬ የሚሠራውን እከታተል ነበር፡፡ የጫማ ስራ ሙያን የበለጠ እያዳበርኩት መጣሁ። በመሀል ስራ መፍታት ስለማልወድ ሌሎች ሙያዎችን እሞክር ነበር፡፡ የተዋጣልኝ የኤሌክትሪክ ባለሙያ ነኝ። እዛው ሰፈር ደረጀ ፀጋዬ የሚባል ኤሌክትሪሽያን ነበር፤ በእድሜ ይበልጠኛል፡፡ እሱ ይዞኝ ይዞር ነበር፡፡ እኔ እና እሱ አዲሱ ገበያ አካባቢ የገጠምነው የኤሌክትሪክ ምጣድ እስከዛሬ ይሰራል። ይሄ እንግዲህ ከ1978 ዓ.ም ገደማ ጀምሮ ማለት ነው። አንድ ሴትዮ በቅርቡ አግኝተውኝ “እስከአሁን የናንተ ምጣድ አለ፤ አክንባሎው ብቻ ዝጐብኝ አስቀየርኩት” ብለውኛል፡፡
በጫማ ሥራ ሙያ ተጨማሪ ሥልጠናዎችን አግኝተሃል?
እሱ ሁሉ  ቀርቶ ብሔራዊ ውትድርና ዘመትኩ እኮ፡፡ ነፍሴንም ያተረፍኩት ኤሌክትሪክሽያን ነኝ ብዬ ነው፡፡ የስንት ሺ ወታደር ምግብ የሚዘጋጅበት ሚንስ ቤት ነበር፤ እዛ ገብቼ በኤሌክትሪሽያንነት መስራት ጀመርኩ፡፡
የት ነበር የዘመትከው?
ኤርትራ፤ ሰሜን ግንባር ነው የዘመትኩት፡፡ ከረን  ሳሊት ግንምባርና በተለያዩ ግንባሮች ተዋግቻለሁ፡፡ በመሃል እጄን ቆሰልኩና ለህክምና አስመራ መጣሁ፡፡ ከታከምኩ በኋላ ማገገሚያ ቦታ ወሰዱኝ፡፡ በርቦሬላ የሚሊሻ ማገገሚያ ይባላል፡፡ በርቦሬላ የጣሊያኖች ምሽግ የነበረ ነው፡፡ እዛ እያለሁ ወይ ኃላፊዎቹ ጠጋ እያልኩ “እንደዚህ እሰራለሁ እኮ” በማለት አንዳንድ ችግሮችን በሙያዬ መፍታት ጀመርኩ፡፡ የአዛዦች ቢሮም እየሄድኩ እሰራ ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ ዝውውር ጠየቁልኝና ወደ ከተማ መጣሁ፡፡
በመጨረሻ ከውትድርና እንዴት ወጣህ?
በ1984 ዓ.ም ደርግ ሲወድቅ ነው የወጣሁት። ከአስመራ ሻቢያዎች አምጥተው ለቀይመስቀል አስረከቡን፡፡ ቀይ መስቀሎች ደግሞ በእግራችን መቀሌ ግቡ አለን፡፡ ከዚያ ከመቀሌ ወደ አዲስ አበባ ገባሁ፡፡ ወደ 700 ኪ.ሜ ገደማ በእግራችን ተጉዘናል።
አዲስ አበባ ምን ገጠመህ?
አዲስ አበባ ስመጣ ስራ የለም፤ አዲስ መንግስት ነው፡፡ ምን ማድረግ አለብኝ ብዬ አሰብኩ፡፡ ያቺ የጫማ ስራ ፍላጐቴ አልሞተችም ነበር፡፡ ራስ ዳሽን ጫማ ፋብሪካ የሚባል ነበር፤ እዛ ሄድኩኝና “ምን ትችላለህ ወታደር ነበርክ አይደል?” ሲሉኝ የምችለውን ሁሉ ነገርኳቸው፤ ተገረሙ፡፡  ድሮም ጫማ ስራ ላይ እንደነበርኩ ገለጽኩላቸው፤ በጫማ ሥራ የሙያ ቋንቋ፡፡ የጫማ ሙያ መሠረታዊ ቋንቋዎች አሉት፡፡ እናም ሙያዊ ትንታኔ ሰጠኋቸው።
ተቀበሉህ?
አዎ፤ በቀን ስድስት ብር ተቀጥሬ መስራት ጀመርኩ፡፡ በሙያው በደንብ ጎለበትኩ፡፡ አንድ አብሮኝ የተማረ ጓደኛዬ… አሁንም “ክሮኮዳይል” የሚባል የጫማ ፋብሪካ አለው፡፡ እሱ የቆዳ ፋብሪካ እንዳለው ሰማሁኝ፡፡ ከረዥም ጊዜ በኋላ ፋብሪካው ሄጄ አገኘሁት፤ የጫማ ባለሙያ መሆኔን ነገርኩት፤ “ወጣሪ ነኝ” አልኩት፡፡ አራት ቀን ያህል አሰራኝና የወንድሙ ፋብሪካ ጋ ወሰደኝ፡፡ ያኔ ለወጣሪ ከ40 ብር በላይ ነበር የሚከፈለው፡፡ የእርሱም ወንድም ቆዳ ፋብሪካ ያለው ትልቅ ሰው ነው። እሱ ጋ ረዥም ጊዜ ሰራሁ፡፡ ጫማ መስፋት ሁሉ ተማርኩ። ጫማ ሰሪ ሲባል በአብዛኛው ሰፊ ነው። እኔ ግን ወጣሪ ነበርኩ፡፡ የቤተሰብ ቤት ስለነበረ እየዘለልኩ ሲንጀር ላይ ነው… የማልሰራው ነገር አልነበረም፡፡ ሁሉንም ጠንቅቄ አወቅሁኝ፡፡ በኋላ ዘርአብሩክ ከሚባል ጓደኛዬ ጋር “ዘርቸር” የተባለ ጫማ ቤት አዲሱ ገበያ አካባቢ ከፈትን፡፡ በትዕዛዝ ጫማ የሚሰራ ማለት ነው፡፡ ሰፈሬ ስለነበር በቀላሉ ገበያ ለመደልኝ። ጓደኛዬ እንዴት ጐበዝ ልጅ ነበር መሰለሽ፡፡ የጫማ ስራ ምስጢር አለው፤ ያልኩት ያኔ ነው፡፡ በፋብሪካ ደረጃ በቅብብል ሲሰራና አንድ ሰው ተጀምሮ እስኪያልቅ ብቻውን ሲሰራው ይለያያል፡፡ አሁን ለደረስኩበት ደረጃ የበቃሁት ከዘርአብሩክ ጋር በመስራቴ ነው፡፡ ገበያ ሄዶ ቆዳውን መምረጥ በራሱ ትልቅ ሙያ ነው፡፡ ራሱ ቆርጦ፣ አዘጋጅቶ፣ ሰፍቶ፣ ወጥሮ፣ ገርዞ፣ አልብሶ፣ ማስቲሽ ቀብቶ፣ አጣብቆ … አንድ ጫማ ለብቻው ሰርቶ ያጠናቅቅ ነበር፡፡ አብዛኛው ባለሙያ ሁሉንም ነገር መስራት አይችልም፡፡ ቆራጭ ከሆነ ቆራጭ ነው፡፡ በቃ!
መቼ ነው የየራሳችሁን የጫማ ቤት ከፍታችሁ መስራት የጀመራችሁት?
አቅም ስናገኝ ነው ለየብቻ መስራት የጀመርነው። ለሁለታችንም 11ሺ ብር እቁብ ደረሰን፡፡ “ዘርቸር” የሚለው ብራንድ ስለሆነ ቁጥር አንድና ቁጥር ሁለት ብለን፣ እኔ አየር ጤና ሄጄ ከፈትኩ፡፡ ጓደኛዬ አዲሱ ገበያ ቀረ፡፡ በኋላ በቻይና ምርቶች የተነሳ ስራው ሲሞት፣ አቋርጨው በሌላ ስራ ተሰማራሁ፡፡
የቻይናን ፉክክር መቋቋም አቃታችሁ ማለት ነው?
ዋናው እኮ የሸማቹ ግንዛቤ ነው፡፡ የእኛን ስራ ገና ሲያዩት “ሎካል ነው” ብለው ነው የሚጀምሩልሽ፡፡ አንድ ገዢ “ይሄ እኮ ሎካል ነው” ሲል “ቀሽም ነው” እንደ ማለት ነው … ይሄ …የዛሬ 13 ዓመት ነው፡፡ አሁን ግንዛቤው ተቀይሯል፡፡
በነገርሽ ላይ መርካቶ ውስጥ ያሉ ባለሙያዎች እጅግ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ ግን ማንም አያውቃቸውም፡፡ ብዙዎቹ ከክፍለሀገር የመጡ ናቸው፡፡ ማሽን የሚሠራውን ስራ በእጃቸው ሲሰሩ ስመለከት፣ ቆሜ ነው ያጨበጨብኩላቸው፡፡ በእርግጥ የፊኒሺንግ ችግር አለ፡፡ የጥራት ቁጥጥር ክፍሉ ስራው ካለቀ በኋላ ምርቱን በደንብ መፈተሽ አለበት፡፡ በተለይ ትልቅ ፋብሪካ ያላቸው በጥብቅ መከታተል አለባቸው፡፡ ጫማ ከመጫሚያነቱ ባሻገር የቅንጦትም ነገር ነው፡፡ ካላማረ ማንም አይገዛሽም፡፡
እንዴት ነው እንደገና ወደ ጫማ ሥራህ የተመለስከው?
እንዳልኩሽ የቻይና ጫማ ሲመጣ ለተወሰነ ጊዜ ሥራውን አቁሜ ወደ ሌላ የሙያ ዘርፍ ገባሁ፡፡ ሆኖም ጫማ የመስራት ፍቅሬ ሌት ተቀን አላስቀምጥ ብሎኝ ነበር፡፡ ለጫማ ስራ እጠቀምባቸው የነበሩ ማሽኖችን ሁሉ አንድ ቀን እመለስባቸዋለሁ ብዬ አስቀምጫቸው ነበር፡፡ ከስራው ብለያይም የማውቀው የጫማ ፋብሪካ እየሄድኩ ሥራዎችን ማየቴ አልቀረም፤ ለአንዳንድ ጓደኞቼም ሞዴል አወጣላቸዋለሁ፤ እቃዬን ሁሉ አውሳቸው ነበር፡፡ እናም ግንኙነቴ አልተቋረጠም፡፡
መስቀል ፍላወር አካባቢ ያለው ሱቄ፣ (አሁን ያየሽው) የሚስቴ ሱቅ ነበር፡፡ የዛሬ 4 ዓመት ከሚስቴ ሱቅ በላይ “ባናቱ ሆቴል” የሚባል ነበር። በርካታ አርቲስቶች ይሰባሰቡበታል፡፡ አንድ ቀን በሆቴሉ በኩል ሳልፍ ብርሃኑ ተዘራ፣ ማዲንጐ አፈወርቅና ሌሎችም አርቲስቶች ተመለከትኩና ገብቼ ተዋወቅኋቸው፤ ተቀራረብን፡፡
የሆነ ቀን ራሴ የሠራሁትን ጫማ አድርጌ ሄጄ፣ እንቁ የሚባል ጓደኛችን… “ይሄ ጫማ ሲያምር” ሲል አደነቀልኝ፡፡ “እኔ ነኝ የሰራሁት” አልኩት፡፡ በሌላ ጊዜም እንዲሁ ሌላ ጫማ ሰርቼ አድርጌ ሄድኩኝ። አሁንም በጣም እንደሚያምር ነገረኝና “ለእኔም ስራልኝ” አለኝ፡፡ በሌላ ቀን አራት ጫማ ስራልኝ ብሎ 4መቶ ብር ቀብድ ሰጠኝ፡፡ በ15ኛው ቀን አንድ ደርዘን (አስራ ሁለት) ጫማዎች ሰርቼ ሄድኩ - በሽሚያ ወሰዱት፡፡
አሁን “አቻሬ ጫማ” ቤት የሆነው የዛሬ አራት ዓመት የሚስቴ ሱቅ ነበር፡፡ ያኔ የሚስቴ ሱቅ አሻንጉሊቶች ላይ የሰራኋቸውን ጫማዎች አስቀምጥ ነበር - ለማስተዋወቅ፡፡ ገና ማስቀመጥ የጀመርኩ ጊዜ ሚስቴ ደውላ፤ “ይሄ ጫማ እዚህ ነው ወይ የሚሠራ ብለው፤ ሁለቱንም በአንድ ጊዜ ወሰዱት” አለችኝ። ከዚያም በተለያዩ ሞዴሎች ጫማ እየሰራሁ ስደረድር ሽሚያ ሆነ፡፡ ያ ዕንቁ ያልኩሽ ጓደኛችን፣ ቅፅል ስም ወጥቶለታል… “አስከፋች” የሚል፡፡ እሱ ነው ገበያውን የከፈተልኝ፡፡
ለምንድነው “አቻሬ ጫማ” ያልከው?
አቻሬ የሚባል ስም ከየት መጣ መሰለሽ … አሸናፊ የሚባል ጓደኛዬ “አቻሬ” ብሎ ይጠራኝ ነበር፡፡ “አቻሬ” ማለት በስፓኒሽ ቋንቋ “እንትና” ማለት ነው። አቻሬ፤ ቸርነት ከሚለው ስሜ ጋር  ይመሳሰላል፡፡ ዛሬ የቅርብ ጓደኞቼ እንኳ ስሜ ይደናገራቸዋል፤ በአብዛኛው “አቻሬ” ነው የሚሉኝ። ለዚያ ነው ጫማውንም “አቻሬ ጫማ” ያልኩት፡፡ አርቲስቶቹ ጓደኞቼ እነ ማዲንጎ ሁሉ “አቻሬ ነው አሪፍ” ብለው ስሙን አፀደቁልኝ፡፡ ኤፍሬም ታምሩ እንደውም የድሮ የህንድ ፊልም ውስጥ “አቻሬ…የሚል ዘፈን አለ” እያለ ያንጎራጉራል፤ ሊቀልድ ሲፈልግ፡፡
የአገሪቱ አርቲስቶች የጫማ ደንበኞችህ ሆነዋል ልበል?
አዎ!! ሁሉም በራሱ ጊዜ ነው መስመር የያዘው። ቴዲ አፍሮ፣ ማዲንጎ፣ ብርሃኑ ተዘራ፣ መሳፍንት፣ ግርማ ተፈራ፣ ጥበቡ ወርቅዬ፣ ጎሳዬ ተስፋየ፣ ግርማ (ጌሪ) .. ደንበኞቼ ናቸው፤ አመሰግናቸዋለሁ፡፡ እንደውም ውጪ አገር ድረስ ይዘውልኝ እየሄዱ ይሸጡልኛል - ከአውሮፓ እስከ አሜሪካ፡፡ ብርሃኑ ተዘራ  መድረክ ላይ  እየዘፈነ.. “ወደ ኢትዮጵያ ግቡ ኢትዮጵያ አድጋለች፤ እንደዚህ ዓይነት ጫማ የሚሰራው የእኛ ወዳጅ ነው” እያለ ያስተዋውቀኛል።
አሜሪካ የሚኖሩ ታዋቂ ኢትዮጵያዊያን አርቲስቶችም የአቻሬ ጫማ ደንበኞች ናቸው ይባላል፡፡ እስቲ እነማን ናቸው?
እነ ታማኝ በየነ፣ ተቦርነህ በየነ፣ አለምፀሀይ ወዳጆ፣ ይሁኔ በላይ … እዛ ላሉ ፓትሪያርክም ሰርቼላቸዋለሁ፡፡ ስማቸውን የማልጠቅስልሽ የሀገራችን ባለስልጣኖች ሁሉ፤ እኔ የምሰራውን ጫማ ያደርጋሉ፤ ደንበኞቼም ናቸው፡፡
በጫማ ስራ ዕውቀት ምን ደረጃ ላይ ነኝ ትላለህ?
ጥሩ ዕውቀት ላይ ደርሻለሁ ብዬ አስባለሁ። በካፒታል ግን ገና ነኝ፡፡ በስራዬ እጠቀማለሁ የምልበት ጊዜ ላይ ነው ያለሁት ፡፡ አሁን ትንሽ ትርፍ፣ በጣም ብዙ ደንበኞች ይዣለሁ፡፡
ዓለማቀፍ የጫማ ደረጃዎችን ታውቃለህ?
በትምህርት ቤት ደረጃ የጫማ ስራን አላውቀውም፡፡ እርግጥ በዓለማቀፍ ደረጃ በጥራትና በብራንድ የሚጠቀሱትን ነገሮች አውቃለሁ፡፡ በመማር ሳይሆን በልምድ ነው ያገኘሁት፡፡  አንድ የውጭ ጫማ አይቼ የጥራት ደረጃውን በደንብ አውቀዋለሁ፡፡ ጫማን በትኖ መልሶ መስራት “የበቃ ባለሙያ” አያሰኝም፡፡ በጫማ ስራ የበቃሽ ከሆንሽ፣ በማየት ብቻ ቁጭ ታደርጊዋለሽ፡፡ የጫማ ስራ ደግሞ መሰረቱ አንድ ነው፡፡
እግር እግር ማየት ትወዳለህ አሉ …
(ሳቅ) በጣም! የሥራው ባህሪ እኮ ነው፡፡ ካሌብ የሚባል አርቲስት ጓደኛ አለኝ፡፡ “ጀመረህ እንግዲህ እግር እግር ልታይ” ይለኛል፡፡ ክለብ ውስጥ በደበዘዘ ብርሃን እንኳ አይኔ ፍልፍል አድርጎ የሚያየው እግር ነው… ጫማ፡፡ አንዴ አንድ ሰውዬ የሚያምር ጫማ አድርጎ አየሁትና  አስፈቅጄው በሞባይሌ ፎቶ አነሳሁት.. በተረፈ በአእምሮ የሚያዝ ነገርም አለ፡፡
የሴት ነው የወንድ እግር  የምታየው?
የሁለቱንም ነው፡፡ ግን የሴት ስልሽ ፍላት ጫማ ከሆነ ነው፡፡ ምክንያቱም ባለተረከዝ (ሂል) ጫማ አልሠራም፡፡ የወንድ ግን በደንብ ነው የማየው፡፡ ሴቶቻችን ሂል ጫማ ነው  በብዛት የሚፈልጉት፡፡ እሱ ደግሞ ብዙ ነገር ይጠይቃል፡፡ ብዙ ጊዜ የአገር ውስጥ ሂሎች ይወዛወዛሉ፡፡ ተረከዝ ያለው ጫማ ለመስራት ይከብዳል፡፡ ውጭ አገር በማሽን ሞቆ ነው የሚሠራው፡፡ እኛ አገር በሚስማር ስለሆነ ቶሎ ይነቀላል፡፡ ያንን ሰርቼ ስሜ እንዲበላሽ አልፈልግም።
አንዳንድ  ጫማዎችህ በዕውቅ አርቲስቶች ስም የተሰየሙ ናቸው፡፡ እንዴት ነው አሰያየሙ?
አንድን ሞዴል መጀመሪያ ባሰራው አርቲስት ነው የሚሰየመው ነው፡፡ የመጀመሪያው ጫማ በስሙ የተሰራለት አርቲስት ማዲንጐ ነው፡፡ ትንሳኤ የሚባል አርቲስትም አለ፡፡ ኤፍሬም ታምሩ ደግሞ አንድ ጓደኛችን የእኔን ጫማ አድርጐት ያይና “ጫማው ያምራል ከየት ነው የገዛኸው?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ “ከጀርመን ሚስቴ ልካልኝ ነው” ይለዋል፡፡ በኋላ ግን እዚሁ እንደሚሠራ ይነግረዋል። እሱም አሰራ፡፡
ምን አስተያየት ሰጠ…ኤፍሬም?
“I am sorry ራሳችንን እኮ ስለማናከብር ነው፤ ከዚህ ወዲያ ምን ጫማ አለ!” ነው ያለው፡፡ አንዷን ሞዴል በተለያየ ከለር እያሰራ ወሰዳት፡፡ የሸዋንዳኝ፣ የቴዲ አፍሮ… ብዙ አርቲስቶች በስማቸው አሰርተዋል፡፡ ከሴት ሳያት ደምሴ፣ ትዕግስት አፈወርቅ አሉ፡፡ ሳያት የምትገርም የዲዛይን ሰው ናት፡፡ በራሷ ዲዛይን ያሰራቻቸው ብዙ ጫማዎች አሉ፤ ፍላት ጫማዎች፡፡
ጫማዎችህ በትላልቅ ቡቲኮች ይሸጣሉ፤ አንተ ከምትሸጠው በሶስት እጥፍ እንደሚሸጡም ሰምቻለሁ…
ቡቲኮች ጫማዎቼን ይወስዳሉ፡፡ ግን የሌላ አገር ስም ጠርተው ነው የሚሸጡት፡፡ እስከ 2ሺ ብር ድረስ የሚሸጡ አሉ፡፡ አየሽ…  “የስፔን ነው” ሲባልና “የኢትዮጵያ ነው” ሲባል አንድ አይደለም። አብዛኛው ሰው የስፔን ነው የተባለውን ነው የሚገዛው፡፡ ሰው የሚገዛው ስሜቱን ነው፡፡ ቦሌ ምድር ላይ “ይህ የኢትዮጵያ ጫማ ነው” ብሎ በድፍረት የገባው “አቻሬ ጫማ” ብቻ ነው፡፡
የምትሰራቸው ጫማዎች ዋጋቸው እንዴት ነው?
ከፍተኛው 650 ሲሆን ዝቅተኛው ደግሞ እስከ ሁለት መቶ ብር ነው፡፡ ከቻይናና ከቱርክ መቶ በመቶ ይበልጣል፡፡ የት ጋ መሰለሽ የምንበለጠው? ግንዛቤ ላይ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን ህዝቡ እየገባው ነው፡፡      
ስንት ሰራተኞች አሉህ?
ስድስት ሰራተኞች አሉኝ፡፡ ስራ ሲበዛ ግን ሰዎች እጨምራለሁ፣ የራሴ ወርክሾፕ አለኝ - ፒያሳ ጣሊያን ሰፈር፡፡
በቀን ስንት ጫማ ትሠራላችሁ?
በዛ ሲባል አስር፤ ትንሽ ሲባል ሁለት እንሰራለን፡፡
ወደፊት እቅድህ ምንድነው?
የራሴ የሆነ ሶል ማምረት እፈልጋለሁ፤ እንደነጃማይካና ከረን ጫማ ፋብሪካዎች፡፡ ለታዋቂ ሰዎች  በስማቸው ጫማ መስራቴን መቀጠል እፈልጋለሁ፡፡ አሁን ለ “ጆሲ ኢን ዘ ሃውስ” (ጆሲ) በስሙ ጫማ እየሠራሁለት ነው፡፡ እሱ መኪናውን እና የመኪና መደገፊያውን በራሱ ስም እያሠራ ነው፡፡  ሌሎችም አሉኝ፤ ቀስ እያሉ ይወጣሉ፡፡

ከኢትዮጵያ ዘውድ ምክር ቤት
P.O Box 320608
Alexandera, Virginia 22320 USA
Email: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
Cellphone:+1(202)32982503

“የንጉሱ ገመና” በሚል ርዕስ ስለታተመው መጽሐፍ ከኢትዮጵያ ዘውድ ምክር ቤት የተሰጠ ይፋዊ መግለጫ

በአሁኑ ጊዜ በሕይወት በሌሉት አቶ ስዩም ጣሰው ተፃፈ ተብሎ የሚነገርለትና በአቶ ግርማ ለማ ለሕትመት የበቃውን “የንጉሱ ገመና/ን/ ዳሰሳ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ያነበብኩት በአግርሞትና በኅዘን ተውጬ ነበር፡፡
መጽሐፉ የቀ.ኃ.ሥ አልባሽ የነበረ ሰውና በዚሁ ሥራው ንጉሱን ከማንኛውም የቤተመንግሰት ሠራተኞች በተሻለ ሁኔታ ሊቀርባቸው ይችላል በሚል መላ ምት ከቀ.ኃ.ሥ ስብዕና ጋር የማይዛመድ ተራ የመንደር ወሬና ስድብን የቋጠረ ዶሴ ሆኖ እንደሚፈረጅ ለአፍታም ጥርጣሬ የለንም፡፡
ከሟች አቶ ሥዩም ጣሰው በተሻለ ንጉሱን በቅርብ የሚያውቁ በሕይወት ያሉ እንደዚያን ዘመን አጠራር “የእልፍኝ አሽከሮች” መጽሐፉ ውስጥ የሰፈሩትን አሉባልታና ስድቦች “ተረት ተረት” ነው በማለት ብቻ ከመወሰን አልፈው ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ የአይን ምስክርነታቸውን ዘገባ በማቅረብ የዜግነት የውዴታ ግዴታቸውን እንዲወጡ በዚህ አጋጣሚ ወገናዊ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፡፡
እዚህ ላይ መታወስ የሚባለው አንዱ ቁም ነገር አለ፡፡ ይኸውም ግፈኛው የደርግ አገዛዝ ቀ.ኃ.ሥ./ን/ በመግደል ብቻ ሳይወሰን የቀ.ኃ.ሥ./ን/ ስምና ሌጋሲ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ጥላሸት ማልበስን ሥራዬ ብሎ ተያይዞታል፡፡ ግፈኛው ሥርዓት የተገረሰሰ ቢሆንም ዘርቶ የሄደው ክፋት፤ ምቀኝነትና ስም ማጥፋት ግን ሕብረሰባችን ውስጥ ተንሰራፍቶ ስለሚገኝ የንጉሱ ገመናም የዚሁ ነፀብራቅ እንደሆነ አያጠራጥርም፡፡
ደግነቱ ግን ዛሬ የቀ.ኃ.ሥ ትክክለኛ ማንነት እውቅና ባገኙ ዓለምአቀፍ የታሪክ ፀሐፊዎች፤ የቀ.ኃ.ሥ ሕይወት ታሪክ ፀሐፊዎች (biographers) እንዲሁም የዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ለሕትመት እየበቃ የሚገኝበት ወቅት ላይ ስለምንገኝ የኢትዮጵያ ሕዝብ የንጉሱ ገመናን ግኝቶች ውድቅ እንደሚያደርገው እምነቴ ነው፡፡
መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአራት አስርተ ዓመታት ለቀ.ኃ.ሥ. ወደር የሌለው ፍቅርና ከበሬታን ቸሯቸው ኖሯል፡፡ የግል ሕይወታቸውም ቢሆን ከሕብረተሰቡ የተሰወረ አልነበረም፡፡ ሰው ናቸውና ስህተት አልሰሩም አይባልም፡፡ ቁም ነገሩ የፈፀሟቸው ስህተቶች ከአስገኟቸው የሶሽዮ ኢኮኖሚክ ድሎች ጋር ሲመዛዘኑ ግን ኢምንት ሆነው ይገኛሉ፡፡ ቀ.ኃ.ሥ ፈሪህ እግዚአብሔር ያደረባቸው አገር ወዳድና ባለ ራዕይ የነበሩ መሪ መሆናቸውን ዛሬ ታሪክ እየመሰከረ ይገኛል፡፡
ለዚህም ነው አንባቢያን ለንጉሱ ገመና ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን እንዳይቸሩት በትህትና ላሳስብ የምፈልገው፡፡ ታሪክ ደግሞ ደጋግሞ የሚያስተምረው ቁምነገር የሰው ስም ጥላሸት በመቀባት የሚገኝ ትርፍ አለመኖሩን ነው፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ
ልዑል ኤርምያስ ሳህለሥላሴ ኃይለሥላሴ  

Published in ህብረተሰብ

       በ1966 ዓ.ም በኢትዮጵያ የተነሳው ሕዝባዊ አመጽ ከዳር እስከዳር እንደሰደድ እሣት በድንገት ተዛምቶ፣ አሮጌውን የዘውድ መንበር ከሥሩ ክፉኛ ነቀነቀው፡፡ ሕዝባዊ ዐመጹ በመንግሥት ዘንድ የፈጠረው እንቅጥቅጥ (Shock) በጣም ብርቱ ከመሆኑ የተነሳ፣ በወርሀ የካቲት የጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድንና የካቢኔያቸውን ስንብት አስከተለ፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ልጅ እንዳልካቸው መኮንን የሰየሙት ካቢኔ፣ አዲስ የሥራ ፕሮግራም ነድፎ በተቃውሞ በተወጠረ የፖለቲካ መድረክ ላይ ጉዞውን ጀመረ፡፡ የአዲሱ ካቢኔ አባላት አሮጌውን የአገዛዝ መንገድ ለመከተል ባለመወሰናቸው ወይም ባለመፍቀዳቸው የተነሳ በአንዳንድ ዘርፎች መንግሥት የነበረው ጽኑ ቁጥጥር እንዲላላ ምክንያት ሆነ፡፡ በዚህ ጊዜ ቀንበራቸው ከላላላቸው እሥረኞች አንዱ የመጻሕፍ ነጻነት ነበር፡፡
በዚህ ታሪካዊ ወቅት፣ መንግስት ያስተዳድራቸው የነበሩት ዕለታዊዎቹ “አዲስ ዘመን” እና “Ethiopian Herald” ጋዜጣ እንዲሁም ሳምንታዊው “የዛሬይቱ ኢትዮጵያ” ጋዜጣ ለመጀመሪያ ጊዜ ከውስጥ ገጾቻቸው “የሕዝብ ነጻ አስተያየት መድረክ” ከፈቱ። አዳዲሶቹ የጋዜጣ መድረኮች የታፈነ ብሶት የሚተነፈስባቸው፣ አዲሱ ለውጥ የሚወደስባቸው፣ መጪው ዘመን ይዞት የሚመጣው ተስፋና በረከት ወይም እልቂትና ውድመት የሚተነበይባቸው ዓይነቶች የሀሳብ መለዋወጪያ መሣሪያዎች ሆኑ፡፡
ነጻነትን በጥቂቱ መለማመድ ይበልጥ ነጻነት መሻትን ማስከተሉ አይቀርም፡፡ እነዚህ አዳዲስ ነጻ መድረኮች የተከፈቱ ሰሞን ይቀርቡ የነበሩት ጽሁፎች ያተኮሩት የየካቲትን ድል በማወደስ፣ ስልጣኑን የለቀቀውን ካቢኔ በመጠኑ በመተቸት ቢሆንም እየዋለ እያደረ መሬት ላራሹን የመሳሰሉ አንኳር ጥያቄዎች አንግበው አደባባይ ወጡ። ጊዜው ፈጣንና ተለዋዋጭ ከመሆኑ የተነሳ ፋታ ያልተገኘበት ሆነ እንጂ ይህ መድረክ የተከፈተበት ወቅት የሰከነ ቢሆን ኖሮ፣ በእነዚህ ጋዜጦች ላይ በነጻነት የሚቀርቡት የበሰሉ ጽሁፎች፣ መንግሥት አገዛዙን ለማስተካከል በተጠቀመበት ነበር፡፡
በዚህ ዘመን ከቀረቡት መጣጥፎች መካከል፤ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ መምህር የነበሩት፤ ዶክተር ጌታቸው ኃይሌ መጋቢት 18 ቀን 1966 ዓ.ም ታትሞ በወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ “ሹመት” በሚል ርዕስ ያቀረቡት ጽሁፍ በዓይነቱም ሆነ በይዘቱ እጅግ የተለየ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ደራሲው በዚያን ጊዜ የዘውድ ሥርዓት ወደማይቀረው ፍጻሜ በለውጥ ኃይሎች በፍጥነት በመገፋት ላይ መሆኑን አጢነው፣ መጪውን ጊዜ ለመቀበል መደረግ ከሚገባቸው የአስተሳሰብ ለውጦች መካከል አንዱ ስለ “ሹመት” ያለውን የተዛባ አመለካከት መቀየር ነው ሲሉ በጽሑፋቸው አትተዋል፡፡
ዶክተር ጌታቸው በዚህ ጽሁፋቸው ስለ ሹመ ት በሿሚው፣ በተሿሚውና በህዝቡ ዘንድ የነበረው ጎታች አስተያየት በአዲስ ለውጥ እና ከወደፊቱ ብሩህ ተስፋ አንጻር መቃኘት አለበት ብለዋል፡፡ “… አንድ ሰው በመሾሙ ምክንያት ክብር ከተጨመረለት፣ የተሾመባቸውም ሰዎች ከሰገዱለት፤ በተጨማሪም በሹመት የተሰጠውን ሥራ ለማከናወን የሚያደርገውን ማስተናበርና ማስተባበር እንደማዘዝ ከቆጠረው፤ ሰው የተፈጠረው በእግዚአብሄር አርአያ ነውና ተሹሞ ጌታ አድራጊ ፈጣሪ ለመሆን ይጥራል። “ኢታምልክ ባዕደ አምላክ ዘእንበሌየ፤ ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ አታምልክ” የሚለውም ስለሚሰማው እሱ ተሸሮ በሱ ምትክ ሌላ ሰው ተሹሞ ሲሰገድለት ሊያይ አይፈልግም…” በማለት ስለ ሹመት ያለው ነባር አስተያየት መቀየር አለበት ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው በሰፊው ፅፈዋል፡፡
ዶክተር ጌታቸው ኃይሌ የአማርኛና የግዕዝ ቋንቋዎች ሊቅ እንደመሆናቸው፣ ይህ ስለ ሹመት የሚያትተው ጽሁፋቸው፤ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው በተዋበ አማርኛ የቀረበና ለዛ ያልተለየው ነበር፡፡
ይሁን እንጂ የአንድ መጣጥፍ መደምደሚያ እንደሆነ በሚታወቀው የመጨረሻ አንቀጽ ላይ ዶክተር ጌታቸው አዲስ ሀሳብ በማንሳት ነው ጽሁፋቸውን የሚያቆሙት፡፡ ይህ አቀራረብ ለተለመደው የጽሁፍ ደንብ እንግዳ ቢሆንም ይሁነኝ ተብሎ በደራሲው የተሰናዳ ዘዴ መሆኑን ለመረዳት የሚቻለው የአንቀጹን ፍሬ ሀሳብ ስንረዳ ነው፡፡ ይህ በመጣጥፍ የመጨረሻ አንቀጽ ላይ የቀረበው አዲስ ሀሳብ፤ “ሹመት” ተብሎ በቀረበው ሰፊ መጣጥፍ በዘዴ ተሸፍኖ የቀረበ ቅመም ነው፡፡
ዶክተር ጌታቸው በመጣጥፋቸው የመጨረሻ አንቀጽ ያቀረቡት ሀሳብ እንዲህ ይነበባል፡- “… በበኩሌ ለውጡ ህልም ነው የሚመስለኝ። በህልሜም ቆማ የኖረች አንዲት መኪና ትታየኛለች። ሁለት ጓደኞች አንዱ ከኋላ ተቀምጦ አንዱ መሪዋን ይዞ ይጫወታሉ፡፡ አንድ ሶስተኛው ሰው በቁጣ መጥቶ፣ የሁለቱን ቦታ ያለዋውጥና መኪናዋን ወደፊት ይገፋታል፡፡ ወዲያው መኪናዋ የቆመችበትን ቦታ ለቅቃ ትንቀሳቀሳለች፡፡ አሁን መኪናዋ የምትሄደው ሞተሯ ስለተነሳ ይሁን ወይም ያ ሶስተኛው ሰው ገፍቷት ወደ ጉዳዩ ስለተመለሰ ይሁን አላውቅም። ሞተሯ አልተነሳ እንደሆን ተመልሳ ትቆማለች፡፡ ቁርጡ የሚታወቀው ከስድስት ወር በኋላ ነው፡፡ ሶስተኛው ሰው የመንጃ ፈቃድ ስለሌለው፣ እሱም ቢሆን እንዲነዳ የፈለገ የለም፡፡ ቁጣው ካልበረደለት ግን ተለማምዶባት የመንጃ ፈቃድ ያወጣባት ይሆናል፡፡ ከምትቆም ይሻላል ማለት ነው እንጂ የወታደር አነዳድ ስም የወጣለት ነው፡፡
ብዙኃኑ የተማረው ክፍል በአገሩ በተነሳው የለውጥ ንፋስ ተወስዶ ያለፈውን እና የአሁኑን ከማየት በስተቀር መጪውን መገመት ባልቻለበት በዚያ ተለዋዋጭ ጊዜ ያለፈውንና የአሁኑን በቅጡ መርምረው ወደፊቱን መመልከት የቻሉ በጣም ጥቂቶች መሆናቸው እሙን ነው፡፡ ከነዚህ ጥቂቶች መካከል ዶክተር ጌታቸው ኃይሌ ጎልተው ይታያሉ። እኒህ ታላቅ ሰው በዚህ “ህልማቸው” ጥርት አድርገው የተመለከቱትም ብሩህ የሆነውን እና ሕዝብ የጮኸለትን የአዲስ ተስፋ ሕያውነት ሳይሆን በጨቋኝ ወታደራዊ አገዛዝ የሚታጀበውን መራሩን የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ ነበር፡፡
ሕልም እንደፈቺው ነው ቢባልም በዚህ “ህልም” የቆመችው “መኪና” ኢትዮጵያ ስትሆን መኪናዋ ውስጥ ተቀምጠው የሚጫወቱትን ሁለት ጓደኛሞች ሳይጠሩትና ሳይጋብዙት በቁጣ ቦታቸውን እንዲለዋወጡ አድርጎ “መኪናዋን” ወደፊት የሚገፋት ሶስተኛው ሰው፣ ያው ወታደር ነው - የወታደር አገዛዝ አምሳያ፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ወታደር ከቁጣ በቀር “የመንጃ ፈቃድ” (ልምድ፣ ችሎታና ብቃት) የለውም፡፡ የሚሄድበትን ሥፍራም የሚያውቅ አይመስልም፡፡ ተሳፋሪዎቹም ሹፌርነቱን አልወደዱትም - ራሱም ጭምር፡፡ የሕልሙ ባለቤት ይህ ወታደር “በመኪናዋ” ተለማምዶባት መንጃ ፈቃድ ያወጣባት ይሆናል ብለዋል፣ ለማጅ የያዘው “መኪና” እንዴት እንደሚንገላታ ለሚያውቅ፣ በእርግጥ እውነታው መራር ሐቅ ነው፡፡
ብዙዎች የአፍሪካ አገሮች ከነጻነት በኋላ እየደጋገመ የደቆሳቸው ጨቋኝ ወታደራዊ አገዛዝ በኢትዮጵያም አመቺ ጊዜ አግኝቶ ሥልጣን ሊነጥቅ እያደባ መሆኑን ዶክተር ጌታቸው ከማንም አስቀድመው ተገንዝበውታል፡፡ ደራሲው ይህንን “ሕልም“ በተመለከቱበት ጊዜ በኢትየጵያ እዚህም እዚያም ብልጭ ድርግም ይል የነበረው የተበታተነ አመጽ፣ በዘውድ መንግሥት ላይ ተነስቶ ደሞዝ ከማስጨመሩ በቀር፣ ይህ ነው የሚባል የተደራጀ ወታደራዊ እንቅስቃሴ አልነበረም። ደርግ የሚቋቋመው ሰኔ 20 ቀን 1966 ዓ.ም ስለሆነ “ህልሙ” ራሱ ደርግን በሶስት ወር ያህል ይቀድመዋል፡፡ እንዲያውም ዶክተር ጌታቸው በህልማቸው “ቁርጡ የሚታወቀው ከስድስት ወር በኋላ ነው” እንዳሉት እውነትም ከስድስት ወር በኋላ ወታደራዊ “አነዳድ” በሙሉ ኃይሉና ጉልበቱ በመላዋ ኢትዮጵያ ላይ ሰፍኖ ለአስራ ሰባት ዓመታት ይቆያል፡፡
ይህ ጽሑፍ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ከታተመ ከ34 ዓመት በኋላ በወጣው ግለ ታሪካቸው (በግል ሕይወቴ ካየሁትና ከታዘብኩት አንዳፍታ ላውጋችሁ፤ 2000 ዓ.ም፤ ኮሌጅቪል፣ ሚኒሶታ) ዶክተር ጌታቸው ይህንን መጣጥፍ ለማቅረብ ምን እንዳነሳሳቸው እንዲህ ገልጸውት ነበር:-
“… እሱ (ልጅ እንዳልካቸው መኮንን) ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ ሳለ፤ ያደቡ ወታደሮች አጠገቡ አሉ። አገሪቱን የሚያስተዳድራት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሁን ሌላ ኃይል ሳይታወቅ፤ ይመሻል ይነጋል። ወታደሮቹ ሥልጣኑን ለሲቪሎች እንደማይሰጡ ስጠረጥር ደነገጥኩ፤ ሰው ለውጥ ለውጥ ማለቱን እንጂ፤ ለውጡን ወታደሮች ሊይዙት እንደሚችሉ፣ ቢይዙትም የሚያሰጋ መሆኑን የሚያመለክት ድምጽ አይሰማም፡፡ … ወታደሮች በሌላ አገር ያደረጉትን ሳስብ ፈራሁ፤ ግን እኔ ማን ነኝ? ማንም ብሆን ለአገሬ መፍራት ብሔራዊ ግዴታዬ ነው… በዚህ ጊዜ እኔም ተሽቀዳድሜ “ሹመት” በሚል ርዕስ ፍርሃቴን ለሕዝብና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አሰማሁ” ብለዋል፡፡
ይህን የዶክተር ጌታቸውን ፍርሃት ሊወድቅ ጥቂት ወራት የቀሩት የዘውድ መንግሥትም ሆነ እንዲወድቅ የሚገፉት አብዮተኞች በቅጡ ተመልክተው አልተጠነቀቁበት ኖሮ፣ ያ ብዙ ተስፋ ተጥሎበት የነበረ ሕዝባዊና ሰላማዊ እንቅስቃሴ ተጠልፎ፣ አገሪቱ አይታ በማታውቀው ጨቋኝና ጨካኝ ወታደራዊ አገዛዝ ሥር ወደቀች፡፡
የሐቀኛ ምሁራን ሚና ከሰፊው ሕዝብ ጋር በስሜት ጎርፍ አብሮ መጉረፍ ሳይሆን ያለፈውን በቅጡ ተመልክቶ ዛሬን ዳስሶ መጪውን መተንበይና ሕዝብን ማንቃት መሆን እንደሚገባው የዶክተር ጌታቸው ጽሑፍ አበክሮ ያስረዳል፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮት የተነሳበትን 40ኛ ዓመት ስንዘክር፤ በሀገራቸው ፍትሕና ዲሞክራሲ እንዲሰፍን የታገሉትን ሠላማዊ ዐርበኞች በማሰብ ብቻ ሳይሆን ይህ ብሩህ ተስፋ እንዳይላሽቅና እንዳይሰረቅ አስቀድመው ነቅተው ያስጠነቀቁትን እንደ ዶክተር ጌታቸው ኃይሌ ያሉትን አርቆ አስተዋይ ታላላቅ ምሁራን በማስታወስ ጭምር መሆን አለበት፡፡

Published in ህብረተሰብ

ከአዘጋጁ-
ከዚህ በታች የቀረበው ፅሁፍ በደርግ መንግስት ጠ/ሚኒስትር በነበሩት ሻምበል ፍቅረስላሴ ወግደረስ ተፅፎ በቅርቡ ለንባብ ከበቃው “እኛና አብዮቱ” የተሰኘ መፅሐፍ የተወሰደ ነው፡፡ በተለይ መጽሐፉን አግኝተው የማንበብ ዕድል ላላገኙ አንባብያን የመጽሐፉን መንፈስ እንዲያገኙት በማሰብ ጥቂት ገፆችን ቀንጭበን አቅርበናል፡፡

ሻለቃ መንግሥቱ በተቀሰቀሰው ስሜት በማዘንና በመተከዝ፣ በመናደድና በመቆጣት ስሜት እየተቀያየሩ በቴፕ በተሰማው ንግግር ላይ በመመርኮዝ ሰፊ ገለጣ አደረጉ፡፡ “የእናንተ ስሜት እንዳይጐዳ እያልን ብዙ ነገር ከመናገር እንቆጠባለን እንጅ የጄነራል አማን እቅድ በጣም ሰፊና አደገኛ ነው” ብለው ንግግራቸውን በመቀጠል “የደርግ አባላትን ወደመጡበት ክፍል መልሶ ደርግን በማፍረስ ከደርግ አባላት ሰባት፣ ከውጭ ደግሞ ሰባት መኮንኖችን ያቀፈ ወታደራዊ ካውንስል በእሳቸው መሪነት እንዲቋቋም ጠይቀውኝ የማልስማማ መሆኔን ነግሬአቸዋለሁ፡፡ ይህ ሃሳባቸው ተቀባይነት ሲያጣ፣ የጦር አዛዦችን በማሰባሰብ መፈንቅለ መንግሥት በማድረግ ሕዝቡ ሆ ብሎ ከሥልጣን ያወረድናቸውን የኃይለሥላሴ መንግሥት ባለሥልጣናትን ከእሥር ቤት በማስወጣት መልሰው በሥልጣን ላይ ለማስቀመጥ እቅድ እንዳላቸው በመረጃ ደርሰንበታል፡፡ ለዚህም ካስፈለገ መረጃውን እናቀርባለን” ብለው ለአጭር ጊዜ ዝም ሲሉ የአዳራሹ ፀጥታ እንደገና ደፈረሰ፡፡ ጉምጉምታና የመገረም ስሜት መሰማት ጀመረ፡፡
ሻለቃ መንግሥቱ በሰጡን መግለጫና በሰማነው የቴፕ ንግግር ሁላችንም ስሜታችን ተነክቷል፡፡ ኃዘንም፣ ፍርሃትም፣ ድንጋጤም፣ ንዴትም በእያንዳንዳችን አዕምሮ ይመላለሳል፡፡ በማንኛውም ሰዓት ልንመታ እንደምንችል ስጋት አደረብን፡፡ ይህንን ስሜታችንን በሚገባ ያጤኑት ሻለቃ መንግሥቱ፤ “አስጊ ሁኔታ ውስጥ ነው የምንገኘው” አሉ፡፡ “ጦሩ ብዙ ጊዜ “የኃይለሥላሴን ባለሥልጣናት አሥራችሁ ትቀልባላችሁ” እያለ ወቀሳ ሰንዝሮብናል ብለው ዝም አሉ፡፡
በከፍተኛ ስሜት ለመገፋፋት ጥቂት የደርግ አባላት እየተነሱ ንግግር ማድረግ ጀመሩ፡፡ “እኛን ለማጥፋት ከተነሱ የኢትዮጵያን ሕዝብ የበደሉትን ማጥፋት አለብን! ካልቀደምናቸው ይቀድሙናል” በማለት ሥጋታቸውን ገለጡ፡፡ እያንዳንዱን ተናጋሪ በመከተል “ትክክል ነው! እርምጃ መውሰድ አለብን! አደገኛውን እንቅስቃሴ ማክሸፍ የምንችለው ቆራጥ እርምጃ በመውሰድ ብቻ ነው” እያሉ አንገታቸውን እየነቀነቁ ድጋፍ የሚሰጡ ነበሩ፡፡ በዚህ ሁኔታ ቅስቀሳው ተፋፋመ፡፡ አንድ ውሳኔ የምንሰጥበት ደረጃ ላይ መድረሳችን ግልጽ እየሆነ መጣ፡፡ ተናጋሪዎች ሁሉ በንግግራቸው መጨረሻ በታሠሩት ሰዎች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ አሳሰቡ፡፡ አብዛኛው ይህን አስተያየት የተቀበለው መስሎ ታየ፡፡ በመጨረሻ ስብሰባውን የሚመሩት ሻለቃ መንግሥቱ፤ ከዚህ በፊት ሲያደርጉት እንደነበረው አሁን እያነሳችሁት ያላችሁት ጉዳይ ዛሬ ከተሰበሰብንበት አጀንዳ ውጭ ስለሆነ አስፈላጊ ከሆነ ወደፊት አጀንዳ ይዘን እንነጋገርበታለን ብለው ማስቆም ሲችሉ ውሳኔ ወደማሰጠት ተሸጋገሩ፡፡
“በእኛ ላይ እያንዣበበ ያለውን አደጋ በስፋት አስተውለናል፡፡ ከዚህ አደጋም ለመውጣት የምንችለው ፈጣንና ቆራጥ እርምጃ ስንወስድ ብቻ እንደሆነ ብዙዎቻችሁ ተናግራችኋል፡፡ ስለሆነም ከታሠሩት የቀድሞ ባለሥልጣናት በተወሰኑት ላይ የመጨረሻውን እርምጃ እንድንወስድ በድምጽ ብልጫ እንወስን” አሉ፡፡ የተቃወመ አልነበረም፡፡ ብዙዎቻችን አንገታችንን በማወዛወዝ የቀረበውን ሃሳብ በምልክት ደገፍን፡፡ ደርግ በስሜት ተገፋፍቶ አንድ አቋም በያዘበት ወቅት አንድ ግለሰብ ለመቃወም ወይም የተለየ አስተያየት ለመስጠት ቢሞክር ከባድ ቅጣት እንደሚደርስበት ስለሚታወቅ፣ ይህን ጉዳይ አስመልክቶ ተቃዋሚ እንኳን ቢሆን ተቃውሞውን ከዝምታ ውጭ በግልጽ ያሰማ አልነበረም፡፡ ይህም ሆኖ ግን የሕግ ባለሙያ ስለሆነ ሊሆን ይችላል ሻለቃ ብርሃኑ ባይህ ብቻ ተነስቶ “በሕግ የተያዘ ጉዳይ ስለሆነ በሕግ ለምን አንጨርሰውም” አለ፡፡ የደገፈው ግን አልነበረም፡፡
ተሰብሳቢው ወደ አንድ አቅጣጫ ማዘንበሉን የተገነዘቡት ሻለቃ መንግሥቱ፤ “የተወሰኑት የቀድሞ ባለሥልጣናት በሞት እንዲቀጡ የምትሰማሙ እጃችሁን አውጡ” አሉ፡፡ ከደርግ አባላት በተጨማሪ የንዑስ ደርግ አባላትና ሌሎችም ተሳታፊዎች በሙሉ ድምፅ የመስጠት መብት ስለተሰጣቸው አብዛኞቹ የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ በመደገፍ እጃቸውን አወጡ፡፡ በጣም ጥቂት የደርግ አባላት እጃቸውን ያላወጡ ቢኖሩም “የምትቃወሙ ወይም ድምጽ የማትሰጡ እጃችሁን አውጡ” ተብለው ሲጠየቁ፣ ከፍርሃት የተነሳ ዝም ብለው አደፈጡ፡፡ በመጨረሻ “በሞት እንዲቀጡ” የሚለው ሃሳብ በሙሉ ድምጽ ተደግፏል ተብሎ ተመዘገበ፡፡ ይህ ውሳኔ እንደተሰጠ ሻለቃ መንግሥቱ ሻለቃ ጌታቸው ሺበሺን በስም ጠርተው “የእሥረኞችን የሥም ዝርዝር የያዘውን መዝገብ አምጣ” ብለው አዘዙት፡፡ መዝገቡም ቀረበ፡
ሻለቃ መንግሥቱ “መረጃ አለ” ብለው ውጥረቱን ረገብ በማድረግ “ጄነራል አማን እጃቸውን እንዲሰጡ ብንጠይቃቸው ፈቃደኛ ሆነው ባለመገኘታቸው ቤታቸው ተከቧል፡፡ ከዚህ በኋላ ማባበሉና መለማመጡ ጥቅም ስለሌለው በሰላም እጃቸውን የማይሰጡ ከሆነ” ብለው በስብሰባው ተሳታፊ የነበሩትን ኮሎኔል ዳንኤል አስፋውን በስም በመጥራት “በሰላም እጃቸውን እንዲሰጡ፡፡ ይህ ካልሆነ ግን እንዲደመሰሱ” የሚል ትዕዛዝ ሰጧቸው፡፡ ኮሎኔሉም ትዕዛዙን ተቀብለው ለማስፈፀም ከስብስባው አዳራሽ ወጥተው ሄዱ፡፡
አሳዛኙ ውሳኔ ከተላለፈ በኋላ “በእያንዳንዱ እስረኛ ላይ እየተነጋገርን ውሳኔ የምንሰጠው ከምሳ በኋላ ይሆናል፡፡ ምሳ ተዘጋጅቶ እዚህ ስለሚመጣ ማንም ሰው ወደ ቤቱ ወይም ወደ ሌላ ቦታ ሊዘዋወር አይፈቀድለትም” ተብሎ ስለተነገረን፣ ደርግ መሰብሰቢያ አዳራሽ ዙሪያ በሚገኙ ክፍሎች ውስጥ ተዘጋጅቶ የሚጠብቀንን እንጀራ በልተን ሻይና ቡናም ጠጣን፡፡ እርስ በርሳችን በቅርብ ስለማንተዋወቅ ምሳ ላይ ሳለን ቀድሞ ያሳለፍነውን ውሳኔ አስመልክቶ ምንም ውይይት አላደረግንም፤ ዝም ማለቱና በሌላ ጉዳይ ላይ መወያየቱ ለሁላችንም የተሻለ አማራጭ ነበር፡፡
ከሰዓት በኋላ በሰባት ሰዓት ሁላችንም በስብሰባው አዳራሽ ጠቅለን ነበር፡፡ ሁለቱም ምክትል ሊቀመናብርትም ተከታትለው ገቡ፡፡ ሻለቃ መንግሥቱ አንድ ትልቅ መዝገብ ይዘዋል፡፡ ወንበራቸው ላይ እንደተቀመጡ መዝገቡን ጠረጴዛቸው ላይ አኖሩት፡፡ አዳራሹ ፀጥታ ሰፍኖበታል፡፡ ድንጋጤና ፍርሃት አስጨንቆናል፡፡ የምናሳልፈው ከባድ ወሳኔ አሳስቦናል፡፡ ሳናስበውና ሳንፈልገው በሁካታ እንድንወስን መገፋፋታችንን የተወሰኑ የደርግ አባላት ተገንዝበውታል፡፡
“ከምሳ በፊት በተስማማንበት መሠረት የእስረኞቹን ስም ዝርዝር በቅደም ተከተል አነባለሁ፡፡ የእያንዳንዱ እስረኛ የሚታወቅ ጥፋቱ ይነገራል፡፡ በመጨረሻ በድምጽ ውሳኔ እንሰጣለን” ብለው ሻለቃ መንግሥቱ የባሕር መዝገቡን ከፈቱ፡፡ ከኪሳቸውም ምልክት ማድረጊያ እስክሪፕቶ አውጥተው ያዙ፡፡ ማንም የተለየ አስተያየት አልነበረውም፡፡ “በአንድ እስረኛ ላይ እዚህ ከተሰበሰብነው ሃምሳ ከመቶ በላይ በሞት ይቀጣ ብሎ እጅ ከወጣበት ይቀጣል፡፡ ከሃምሳ በመቶ በታች ከሆነ ግን ይድናል” ብለው ስለአወሳሰኑ ማብራሪያ ሰጡን፡፡
ከዚህ በኋላ ስም መጥራቱ ተጀመረ፡፡ በመጀመሪያ የአቶ አክሊሉ ሃብተወልድ ስም ተጠራ፡፡ ሁሉም ያውቃቸዋል፡፡ ለረጅም ጊዜ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል፡፡ ለኢትዮጵያ ኋላቀርነት፣ ለሕዝቡ ድህነት፣ በወሎ ለደረሰው ረሃብና እልቂት ተጠያቂ እንደሆኑ ከተሰብሳቢዎቹ ውስጥ የተወሰኑት እየተነሱ ተጨባጭ ማስረጃ ይኑረው አይኑረው የማይታወቅ ወንጀል ደረደሩባቸው፡፡ ከዚያ “በሞት እንዲቀጡ የምትስማሙ እጃችሁን አውጡ” ተባለ፡፡ አብዛኛው ተሰብሳቢ እጁን አወጣ፡፡ ከሃምሳ ከመቶ በላይ መሆኑ በቆጠራ ተረጋገጠ፡፡ “በሞት እንዲቀጡ ተወስኗል” ብለው ሻለቃ መንግሥቱ ምልክት አደረጉ፡፡ በዚህ ዓይነት ፍርድ መስጠቱ እስከምሽቱ አንድ ሰዓት ድረስ ቀጠለ፡፡
***
ኢህአፓና ወጣቱ የኅብረተሰብ ክፍል
ኢሕአፓ የተመሠረተው፣ ከላይ እስከታች የተዋቀረውም በአብዛኛው በወጣቶች ነበር፡፡ ከሠራተኛው ከመምህራንና ከተማረው ኅብረተሰብ ክፍል ወጣቶች ተመልምለው በኢሕአፓ በተደራጁ የሙያ ማህበራት ውስጥ በአመራር ሰጭነትና በተራ አባልነት ያሰማራቸው የነበሩት ወጣት ተማሪዎች ነበሩ፡፡ ወጣት ተማሪዎች ምን ዓይነት ለውጥ እንደተደረገ እንኳን በደንብ ሳይረዱ “ለውጡን ያቀጣጠልን የለውጥ ሐዋሪያ ነን” ብለው ስለሚያምኑ፣ ግምባር ቀደም ኃይል ነን ብለው ስለሚገምቱ፤ ሞትን እንኳን ሳይፈሩ ከማንኛውም አደገኛ ኃይል ጋር በጀብደኝነት ፊት ለፊት ይጋፈጣሉ፡፡ የወጣት ተማሪዎችን መሠረታዊ ድክመት ብዙም ጥያቄ የማያቀርቡና ማብራሪያም የማይፈልጉ በመሆናቸው፣ በድርጅታዊ ዲሲፕሊን ሽፋን የድርጅት መመሪያ ነው አድርጉ ወይም ፈጽሙ ተብሎ የሚመጣላቸውን ትዕዛዝ ባለማወላወል ተግባራዊ ስለሚያደርጉ ኢሕአፓ ፍላጐቱን ለማሟላት ምቹ መሣሪያ ሆነው አገኛቸው፡፡
ደርግ “ለሕዝቡ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አስተዋጽኦ ያደርጋል” ብሎ የሚወስደውን ማንኛውንም እርምጃ ኢሕአፓ አቃቂር በማውጣትና በማጥላላት የወጣቱን ስሜት የሚቀሰቅሱና የሚስቡ መፈክሮች በማንሳት፣ ወጣት ተማሪዎችን በከፍተኛ ደረጃ ለመመልመል በቃ፡፡ አብዛኛውን ወጣት ተማሪ ለመመልመል የቻለው በዕድገት በኅብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ ወቅት የከተማ ቦታና ትርፍ ቤቶች እንዲወረሱ የሚደነግገው አዋጅ ከወጣ በኋላ ነው፡፡
ኢሕአፓ ወጣቱን አባልና ደጋፊ ለማድረግ የበቃው በማሳመንና በፈቃደኝነት ብቻ አልነበረም፡፡ በማንኛውም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ተሳታፊ ለመሆን ፍላጐት ያልነበረው ማንኛውም ወጣት፤ ኢሕአፓ ለሚያካሂደው እንቅስቃሴ ጠቃሚ መስሎ ከታያቸው በማስገደድ ወይም በማስፈራራት ወይም ስም በማጥፋት ሳይወድ በግድ አባል ያደርጉታል ወይም የሚሰጡትን ሥራ እንዲፈጽም ያስገድዱታል፡፡

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሰላምታዬን ማስተካከል አለብኝ መሰለኝ…“ሠፈራችሁ መብራት አለ?”
ይቺን ስሙኝማ…ሦስት ሆነው አንዲት ደከም ያለች ‘ካፌ’ ውስጥ ሻይና ቦምቦሊኖ ነገሮች ይቀማምሳሉ፡፡ እናላችሁ፣ አንደኛው መቶ ብር ከኪሱ ያወጣና ይከፍላል፡፡ (እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ከዓመታት በፊት ማለትም ያኔ የብሩ ቁጥርና የመግዛት አቅሙ አቅም ተቀራራቢ በሆኑበት ዘመን ቢሆን ኖሮ…አለ አይደል…“መቶ ብሩን ከኪሱ መዠረጠው!” “አታምነኝም፣ መቶ ብሩን ከኪሱ ላጥ ሲያደርገው የደነገጥነው መደንገጥ!” ነበር የሚባለው!)
እናላችሁ…የሆኑ ለቲፕ የተተዉ የሚመስሉ ሳንቲሞችና የተጎሳቆሉ አንድ፣ አንድ ብሮች መልስ ተብለው በሳህን ላይ ይመጡላችኋል፡፡ እና ከፋይ ምን ቢል ጥሩ ነው… “መቶ ብር በሻይና በቦምቦሊኖ ብን ትበል! በቃ… መቶ ብራችን እኮ ሁሴን ቦልት ሆና አረፈችው!”
እውነትም ሁሴን ቦልት! አለች ስትሏት ውድም! የምር... የዘንድሮ መቶ ብር እኮ “ምን ገዛሁባት!” ሳይሆን “የት ጥያት ይሆን!” የምታሰኝ ነች!
እንግዲህ በዓልም እየመጣ ነው… ይሄኔ ‘ሞኞቹ’ ነጋዴዎች አሮጌ መሀረብ ይሁን የመጸዳጃ ቤት ወረቀት ያሳበጠው ኪሳችንንና ለምናልባቱ “ሆዴን ቢረብሸኝ…” ብለን ድንገተኛ ቢጤ የቋጠርንበት መቀነታችን በብር የተሞሉ ይመስላቸዋል፡፡ ባዶ ነው! እንደውም…አለ አይደል…ኪስን ‘ለመጋዘንነት’ ማከራየት ቢቻል ኖሮ፣ ስንቱ የሀበሻ ልጅ ፍራንክ በፍራንክ ይሆን ነበር!
ስሙኝማ…አንዳንዴ ነገረ ሥራችን እኮ ለፈለገ ‘ጥይት’ የሆነ ተመራማሪ እንኳን ቢሆን ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ችግር መሀል ከፍስኩ በኋላ በየክትፎ ቤቱ የሚኖረውን ግፊያ ስታስቡት…ድንገተኛ ጎብኚ “ኧረ እነሱ ጥጋብ በጥጋብ ናቸው፣” ቢል አይገርምም፡፡ (እንደውም…“አመጋገባቸው የሁለት ዲጂት ዕድገት አሳይቷል ባይል ነው!”  ቂ…ቂ…ቂ…)
እናላችሁ…ምድረ ምግብ ቤት ሲሳይ ሊወርድለት ነው፡፡ የምር ግን የብዙ የምግብ ቤቶቻችን ነገር ግርም አይላችሁም…የምግብ ዝርዝሩ ላይ ሠላሳ ሦስት ምግብ አይነቶች ተደርድረዋል፡፡ የምታገኙት ግን ግፋ ቢል አምስትና ሰባቱን ነው፡፡
“ስቴክ አለ?”
“ስቴክ የለም! እስቲ ጠይቄ ልምጣ!”
“የቤቱ ስፔሻል ምን ምን አለበት?”
“እ…ጠይቄ ልምጣ፡፡”
“ጠይቄ ልምጣ…” የሚያበዙ አስተናጋጆች፤ “ጠይቄ ልምጣ…” የሚለውን ሀረግ እንዳይጠቀሙ እገዳ ይጣልልን፡፡ (መቼም ለ‘እገዳ’ና ‘ክልከላ’ የሚችለን የለም አይደል!)
 ስሙኝማ…እግረ መንገዴን…ምን የሚያካክሉት ሆቴሎች በእንግሊዝኛ የሚጽፏቸው የምግብ ስሞች ‘በምን ቋንቋ እንደተጻፉ’ ይነገረን! ቂ…ቂ…ቂ… ገና ለገና “የፈረንጅ አፍ አያውቁም…” እየተባለ አታሞኙና!
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የሞኝነት ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ… (ይህን ክፍል ከአሥራ ስምንት ዓመት በታች ማንበብ የተከለከለ!…ቂ…ቂ…ቂ…) ሰውየው ለካስ ከሰው እርቆ ከርሞ ኖሯል፣ እናላችሁ… ራሱ ላይ ‘ያልወጣበት’ ነገር የለም! ታዲያላችሁ…አንድ ቀን ሰው በሌለበት አካባቢ የሆነች ግመል ያይና ‘እርኩስ መንፈስ’ ያድርበታል፡፡ (ዝርዝሩን በቦታ ጥበት ምክንያት አልጻፍነውም!)
እናማ… ግመሊት ሆዬ ያዝ ሲያደርጋት ትሸሻለች፣ ያዝ ሲያደርጋት ትሸሻለች፡፡ እሱዬው ሊፈነዳ (ጭንቅላቱን ለማለት ነው!) ምንም አይቀረው፡፡ ይሄኔ ‘የከፈተውን ጉሮሮ ሳይደፍን’ የማያድረው ፈጣሪ ምስጋና ይግባውና አንዲት ሴት ብቅ ትልላችኋለች፡፡
“እባክህ አንድ ውለታ እንድትውልልኝ ፈልጌ ነው…” ትለዋለች፡፡ እሱዬውም “ምን ላድርግልሽ?” ይላታል፡፡ እሷም “አገሬ የምደርስበት ገንዘብ አጠረኝ፣ ትንሽ ብትረዳኝ…” ትለዋለች፡፡ ከዛ ምን ይላታል… “ገንዘቡን ብሰጥሽ የፈለግሁትን ነገር ታደርጊልኛለሽ?” ይላታል፡፡
እሷም “በደንብ አድርጌ…” ትለዋለች፡፡ እሱም ለማረጋገጥ እንደገና… “ምንም ነገር ቢሆን ያልኩትን እሺ ብለሽ ትፈጽሚያለሽ?” ይላታል፡፡ እሷም “ምንም ነገር ቢሆን እፈጽማለሁ፣” ትለዋለች፡፡ ከዛላችሁ…ገንዘቡን ይሰጣታል፡፡
እሷዬዋ ገንዘቧን ከተቀበለች በኋላ… “እሺ፣ ምን እንድፈጽምልህ ነው የምትፈልገው?” ስትል ትጠይቀዋለች፡፡
አጅሬው ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው… “አንድ ጊዜ ግመሏን እንዳትነቃነቅ ያዥልኝ!”
እኔ የምለው…የፈለገው አይነት ቢሆን እዚህም የሚደርስ ሞኝነት አለ? ነው ሰውየው ስለ ‘ባዮሎጂ’ የሚያውቀው ነገር የለም!
እናላችሁ…በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ሞኝነትን የሙጥኝ ያልን ያለን አለን፡፡ ደግሞላችሁ “ግመሏን እንዳትነቃነቅ ያዥልኝ!” የምንል አይነት ሞኞች የሚያደርጉን ግለሰቦችና ተቋሟት መአት ናቸው፡፡
አሳላፊውን ትጠሩታላችሁ… “ያዘዘኩት እኮ ጭቅና ጥብስ ነው…”
“እሱ እኮ ጭቅና ጥብስ ነው፡፡”
የቀረበው ሥጋ እኮ አይደለም ሊለሰልስ…ምን አለፋችሁ፣ ኤክሲሞዎች ከሦስት መቶ ዓመት በፊት በረዶ ውስጥ የቀበሩት የጎሽ ሥጋ እንኳን እንደዛ አይጠነክርም፡፡ እናማ… “ግመሏን እንዳትነቃነቅ ያዥልኝ!” የምትሉ ሞኝ ሲያደርጓችሁ አያበሽቅም!
“ድርጀቱ ምርቱን ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው…” ይሏችኋል፡፡ ወይ ምርት ማሳደግ!... ሰውየው ካለፉት አሥራ አምስት ቀናት ውስጥ አሥራ አንዱን እኮ በስብሰባ ነው ያሳለፉት!
ዘንድሮ እንደሆነ መሰብሰቢያ ምክንያት አይጠፋም፡፡ የምር እኮ… አለ አይደል… ስብሰባ ራሱን ችሎ ‘የኤክስፖርት ምርት’ ቢሆን ኖሮ ባዶ አቁማዳችንን አንጠልጥለን በየጄኔቫውና በየዋሽንግተኑ  “እርጠቡን!”  “ጽደቁብን!” እያልን ባልተንከራተትን ነበር፡፡
እናላችሁ…አይደለም ምርት ሊያድግ… አንዲት ደቂቃ ሳይሠሩ የዛጉ መሣሪያዎች በሞሉበት “ግመሏን እንዳትነቃነቅ ያዥልኝ!” የምትሉ አይነት ሞኞች ሲያስመስሏችሁ የምር ያበሽቃል፡፡  
ብዙ ጊዜ ሪፖርት ምናምን የሚሏቸው ነገሮች ሲቀርቡ… “በሠራተኞቹ መካከል ያለው ከፍተኛ የሥራ ፍቅር…” ምናምን የሚሏት ነገር አለች፡፡ አይደለም የሥራ ፍቅር ሊኖር…አለ አይደል… ሰዉ ተናክሶ፣ ተናክሶ ምናልባትም… “በሠራተኞች የእርስ በእርስ ቁርሾ ሦስተኛ ዓለም ጦርነት መነሻ የሆነችው የመጀመሪያዋ አገር…” አስብለው የአልጀዚራ የዘጋቢ ፊልም ሲሳይ ሊያደርጉን የሚችሉ ናቸው እኮ። ሰዉ ሥራ ከመሥራት ይልቅ ሁሉም ሰላይ፣ ሁሉም ተሰላይ በሆነበት “የሥራ ፍቅር…” ምናምን ነገር እየተባለ “ግመሏን እንዳትነቃነቅ ያዥልኝ!” የምትሉ አይነት ሞኞች ሲያስመስሏችሁ የምር ያበሽቃል፡፡  
ደግሞ ሌላ አለላችሁ፡፡ “እየተከናወኑ ያሉ ሁለንተናዊ የዴሞክራሲ፣ የልማትና ፍትህ ተግባራት ሁሉን አሳታፊ በሆነ መልኩ…” (ስለደከመኝ አቋረጥኩት) የሚባል እንደ ዕለታዊ ጸሎት ተደጋጋሞ
የምትሰሙት ነገር አለ፡፡ እኔ እንደውም ምን ይመስለኛል መሰላችሁ… አንዳንዴ ሳስበው የሰው ልጅ ላይ ተጠናቆ የተዘጋጀ ‘ሶፍትዌር በመጫን’ ዓለምን እንደምንቀድም ማንም ያየልን የለም፡፡ አሀ…ሶፍትዌር ካልሆነ እስከ ነጠላ ሰረዝ ድረስ ተመሳሳይ ነገር መናገር የሚቻለው በምን ተአምር ነው!  
እናላችሁ… የማርያም መቀነትን በአሥር እጥፍ የሚያስከነዳ ዓረፍተ ነገር የሚያነበንቡት ‘ሶፍትዌር እንደተጫነባቸው’ የሚጠረጠሩት (ቂ…ቂ…ቂ…) ዴሞክራሲ ምናምን ማለት ተጀምሮ የሚያልቅው “ስሙኝማ…” እያሉ በመጻፍ ብቻ የሚመስላቸው አይነት ናቸው። እናማ… በለመድናት ‘ቋንቋ’… “ግመሏን እንዳትነቃነቅ ያዥልኝ!” የምትሉ አይነት ሞኞች ሲያስመስሏችሁ የምር ያበሽቃል፡፡  
የምር ግን ምንም አይየነት ነገር ቢያደርጉን ተፍቆ የማይለቅ፣ ታጥቦ የማይጠራ… ‘ሞኝነት’ ተሸክመን የምንዞር መአት ነን፡፡
እንትናዬ…ግመሏን እንዳትነቃነቅ ያዥልኝማ!  ማለትም…ስለ ባዮሎጂ የሚያስረዳ ደግ ሰው እስካገኝ ድረስ!
መልካም የበዓል መዳረሻ ሰሞን ይሁንላችሁ።
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Published in ባህል
Page 8 of 13